ናፋቂ ከሆንኩ ፍትህና የህዝብን ዴሞክራሲ ናፋቂ ነኝ
የአገራችን የሚዲያ አወቃቀር በአንድ አካል የሚታዘዝ ነው
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤በተለያዩ የፖለቲካ መድረኮች በሚሰነዝሯቸው ጠንካራ ትችቶች ይታወቃሉ፡፡ ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት የነፃውን ፕሬስ ሁኔታ አስመልክቶ በሬድዮ ፋና በተዘጋጀው ውይይት ላይም ተሳትፈዋል፡፡ ጋዜጠኛ ናፍቆት ተስፋዬ ከዶ/ር ዳኛቸው ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ የገባበት ስለጠፋው የዩኒቨርሲቲ የኮንትራት ውል፣ ስለፍርድ ቤት ነፃነት፣“በኢትዮጵያ ውስጥ የመናገር ነፃነት የለም”--- ስለማለታቸውና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በስፋት አነጋግራቸዋለች፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር የተዋዋሉባቸው ሰነዶች በሙሉ መጥፋታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
ከዚህ ቀደም ባልሳሳት---ከአንድ ዓመት ከሁለት ወይም ከሶስት ወር በፊት ይመስለኛል “60 ዓመት ስለሞላህ ኮንትራት ያስፈልግሀል” ተብዬ የሁለት ዓመት ኮንትራት ፈርሜ ነበር፡፡ የዚህ ኮንትራት ግልባጭም ለእኔ የተሰጠኝ ሲሆን በተጨማሪም ለፍልስፍና ዲፓርትመንቱ፣ ለዲኑ ቢሮና ለምክትል ፕሬዚዳንቱ እንዲሁም ለፐርሶኔል ቢሮ በአጠቃላይ አምስት ቦታ ተላከ፡፡ ሆኖም አምስቱም ደብዳቤዎች ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ሌላው ቀርቶ እኔም ቢሮ የነበረው ሊገኝ አልቻለም፡፡ እንዲያውም የዲፓርትመንት ኃላፊው፣ የኮሌጁ ዲኑና፣ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ቢሮም “ሲጀመርም ደብዳቤውን ስለማየታችን ትዝ አይለንም” የሚል መልስ ነው የሰጡት፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ ይሄ ሰውዬ ኮንትራት ሳይኖረው ከአንድ ዓመት በላይ አስተማረ እስከ ማለት ደረሱ፡፡ እኔም በበኩሌ፣“ኮንትራትህ እድሳት ያስፈልገዋል ተብዬ ሂደቱ አራት ወር ስለወሰደ፣ ለአራት ወራት ደሞዜ ታግዶ ነበር፣እድሳቱ ሲያልቅ ደሞዜ መለቀቁ ምልክት አይሆናችሁም ወይ?” ብላቸው ያመነኝ ሰው አልነበረም፡፡ ፐርሶኔል ክፍሎች ግን ፍቃዱ ባይራዘምለት ከአራት ወር በኋላ ደመወዙን አንለቅም ነበር ብለው ተከራከሩ፡፡ ሆኖም የነሱንም ሀሳብ የሚያዳምጣቸው አላገኙም፡፡ አሁን ለጊዜው በዝርዝር ለማስረዳት ባልዘጋጅም፤በጥቅሉ ሰነዱ ባንዳንድ ሰዎች እርዳታ ፐርሶኔል ቢሮ ከሳምንት በላይ ተፈልጎ ተገኝቷል፡፡ይህ ኮንትራት ባይገኝ ኖሮ ምናልባት ከሥራ ለመሰናበት እደርስ ነበር፡፡ አሁን ግን የኮንትራቱ ውል በመገኘቱ ምክንያት እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ማስተማር እችላለሁ ማለት ነው፡፡  የኮንትራቱ ውል ከመገኘቱ  በፊት ግን ደብዳቤ ፅፈውልኝ ነበር፡፡
ምን ዓይነት ደብዳቤ?
“በአንተ እጅ ያለውም ሆነ ሌላው ክፍል የነበረው የኮንትራት ውል ስለጠፋ፣ የተሰጠህን የዓመት ፈቃድ ለጊዜው ይዘነዋል” የሚል፡፡ የእኔ ክርክር ጭብጥ ሁለት መንገድ የተከተለ ነው፡፡ አንዱ የኮንትራት ውሉ ሲሆን ሁለተኛው የዓመት ፈቃዱ ነው፡፡ የኮንትራት ውሉ ተገኘ፡፡ በመጀመሪያ የዓመት ፈቃዱን የያዙት የኮንትራት ውሉ ስለጠፋ ነበር፡፡ ወረቀቱ ሲገኝ ደግሞ የዓመት ፈቃዱ መለቀቅ ሲገባው አሁን ሌላ ሰበብ አመጡ፡፡ እድሜህ ስልሳ ዓመት ስለሞላና የጡረታ ሂደቱ በደንብ ተካትቶ ፋይልህ ውስጥ ስለሌለ፣ የዓመት ፈቃድህን ሰርዘነዋል አሉኝ፡፡ አሁን “ከሰስፔንሽን” ወደ “ካንስሌሽን” ሄደዋል ማለት ነው፡፡ የዓመት ፈቃዴን ባለፈው ሳምንት ነበር የምጀምረው፣ እሱን ተነጥቄያለሁ እልሻለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ ማለት አልፈልግም፡፡
ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት በሬዲዮ ፋና ላይ በነፃው ፕሬስ ዙሪያ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡  እርስዎም በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የውይይቱ ፋይዳ ምንድን ነው ይላሉ?
እንግዲህ አንድ የሬድዮ ጣቢያ ፕሮግራም ሲያዘጋጅ ፋይዳውን የሚያውቀው ሬዲዮ ጣቢያው ራሱ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከሰጡን ርዕስ ተነስቼ አንዳንድ ነገሮችን ለመገመት አያዳግተኝም፡፡ ርዕሱ እንግዲህ በኢትዮጵያ ያሉ የነፃው ፕሬስ ጋዜጦችና መፅሄቶች ምን ይመስላሉ? እንዴትስ ሊሻሻሉ ይችላሉ? የሚል ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ስመለከተው የግሉን (ነፃውን) ፕሬስ በተጠናከረ ሁኔታ መተቸት ይፈልጋሉ፡፡ ሁለተኛ ከመንግስት ጋር ያልተያያዝን ሰዎች በውይይቱ ብንሳተፍ፣ ትችቱ ይሰምራል የሚል አስተሳሰብም ነበራቸው፡፡ ሌላው እኔን በግሌ ብትጠይቂኝ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጆርናሊዝም እና ኮሚዩኒኬሽን ዲፓርትመንት በቅርቡ  ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ “በኢትዮጵያ ውስጥ የመናገር ነፃነት (Freedom of Speech) የለም” ብዬ ሽንጤን ገትሬ ተከራክሬ ነበር፡፡ ይህም በዩቲዩብ እና በተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎች ስለተሰራጨ፣ ለዚህ ምላሽ በመስጠት ያንን የተሰራጨ ሃሳብ ለማምከን እቅድ የነበራቸው ይመስለኛል፡፡ እኔ በሁለት ፕሮግራሞች ላይ ነው የተሳተፍኩት፣ እነሱ ግን ቀደም ብለው የጀመሩት ይመስለኛል፡፡
ውይይቱ ላይ ተጋብዘው ነው ወይስ በራስዎ ተነሳሽነት?
የሬድዮ ፋናው አቶ ብሩክ ከበደ ጋብዘውኝ ነው የተገኘሁት፡፡
በውይይቱ ላይ“ዶ/ር ዳኛቸው ስሜታዊ ሆነው ነበር”የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የሚል ትችትም ተሰንዝሮቦታል፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
የስሜታዊነቱን ነገር ያመጡት እንኳን እነሱ ናቸው፡፡ ስድብና ዘለፋውን በመጀመር እነሱ ይቀድማሉ፡፡ “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” ለሚለው በእውነቱ በናፍቆት ደረጃ ፍትህ ናፋቂ ነኝ፡፡ ዴሞክራሲና የህዝባችንን ነፃነት ናፋቂ ነኝ፡፡ የዱሮ ሥርዓት ናፋቂ የሚሉኝ “አሁን ያለንበት ወርቃማው ጊዜ ነው” የሚሉ ዜጎች ናቸው፡፡ “ያለፈው ስርዓት ናፋቂ” የሚለው አባባል ሆን ብሎ ሰዎችን ለማሸማቀቅ የተፈጠረ ቃል ነው፡፡ በሌላ መልኩ የአሁኑ ስርዓት እኮ በጣም የተሻለ ነው ለማለት ነው፡፡ እኔ የዛሬ 40 ዓመት ወደ ኋላ ሄጄ ለማወዳደር የፈለግሁት አጠቃላይ ሥርኣቱን ሳይሆን የመናገር ነጻነትን በተመለከተ ርዕስ ብቻ ነበር፡፡ ይህንንም ለመናገር የዕድሜ ባለጸጋም ነኝ፡፡ “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” በሚባልበት ጊዜ አንድ ዓመት  ዩኒቨርሲቲ ተምሬያለሁ፡፡ ያኔ የተሻለ የመናገር ነፃነት ነበር ብያለሁ፡፡ ይህንን አባባሌን አሁንም እደግመዋለሁ፡፡ “በአፄው ጊዜ የፈለግነውን ለመተቸት የዩኒቨርሲቲው ህግ ይፈቅድልናል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ መዲና ነበር፡፡ ዛሬ ግን ተነስተሸ አንድ ፖለቲካዊ የሆነ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ አስተያየት ብትሰነዝሪ ከጸጥታ ኃይሉ የሚጠብቅሽ ችግር ይኖራል፡፡” ስላልኩኝ ነው “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የተባልኩት፡፡ ይሄ አይነተኛ የሆነ የካድሬዎች ማስፈራሪያና በነፃነት የሚናገሩ ሰዎችን ማሸማቀቂያ መንገድ ነው፡፡ እኔ እኮ የድሮ ትዝታ አለኝ፣ ልናፍቅም እችላለሁ፡፡
ለምሳሌ ከድሮው ስርዓት ምን ምን ይናፍቅዎታል?
ለምሳሌ የእንግሊዝ ፈላስፋ ኤድመን በርክ “Familiarity” የሚል ስለ ትዝታ ያነሳው ሀሳብ አለ፡፡ “ፋሚሊያሪቲ” ምንድነው? መተዋወቅ፣ ያሳለፍነው ትዝታ፣ትውስታ ማለት ሲሆን፤እንደ አርሱ አቀራረብ በአንድ ጉዳይ ላይ ስለተዋወቅን ብቻ መናፈቅ፣ የሰው ልጅ ባህሪና ፀጋ ነው ይላል፡፡ ገባሽ? እኔ የጥንቱን የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ እናፍቃለሁ፣ የፖሊስ ኦርኬስትራንም እንዲሁ፡፡ ዛሬ አንድ ኪቦርድ አስቀምጠው የሚዘፍኑትን ከምሰማ የእነዚያን ኦርኬስትራዎች ሥራ ብሰማ እናፍቃለሁ፡፡ የፈረሱትን የድሮ ሲኒማ ቤቶች--- እነ ሲኒማ አድዋን እናፍቃለሁ፡፡ የድሮውን የመድረክ ተውኔት እናፍቃለሁ፡፡ የድሮው የክብር ዘበኛ አለባበስ ከፈረሳቸውና ከነማዕረግ ልብሳቸው ትዝ ሲለኝ እናፍቃለሁ፡፡ እንዴ ብዙ ብዙ የምናፍቀው ነገር አለኝ--- እሱን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ በሰፈሬ ሳልፍ አሁን የደረቀው ቀበና ወንዝ ከነሙላቱ ይናፍቀኛል፣ ድሮ ለምሳሌ ሆቴል ገብተን ክትፎ በ75 ሳንቲም “ቅቤ ይጨመር?” እየተባለ የምንበላው ይናፍቀኛ…..እንዴት ያለ ነገር ነው! ድንች በሥጋ ወጥ 15 ሳንቲም የነበረበት ጊዜ ይናፍቀኛል፡፡ የድሮዎቹ አስተማሪዎቼ ይናፍቁኛል፡፡ ታዲያ የድሮውን መናፈቅ ምን ነውር አለው? ምንስ አድርግ ነው የምባለው?
እርስዎም “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የሚለው አነጋገር የካድሬ ቋንቋ ነው ብለዋል፡፡ ምን ማለት ነው?
ካድሬዎች ሁልጊዜ ያለንበት ስርዓት ነው ወርቃማው ይላሉ፡፡ ያለፈው በጠቅላላው አይረባም ባይ ናቸው፡፡ ሲያስተምሯቸውም እንዲህ እንዲያስቡ ነው፡፡ እኔን “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” ያለኝም ወጣት በዚያ ስለወጣ ነው፡፡ በጣም ልጅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም በሌላ ፕሮግራም ላይ አግኝቼዋለሁ፡፡ ያን ጊዜ አቦይ ስብሀት ባሉበት በጣም ሀሳባዊ የሆነ፣ የአሁኑን ሥርዓት “ፍየልና ነብር የሚሳሳሙበት” ወርቃማ ጊዜ እንደሆነ አድርጎ ሲያወራ፣ “አንተ ልጅ እስኪ አቦይ ስብሀት ጋር ዝም ብለህ አንድ ሁለት ዓመት አሳልፍ፣ ያኔ ፖለቲካህ መሬት የረገጠ ይሆናል” በማለት መክሬው ነበር፡፡
በእርሶ እይታ አሁን ያሉት በጣት የሚቆጠሩ የግሉ ፕሬስ ውጤቶች ምን ይመስላሉ?
እኔ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ማስቀመጥ የፈለግሁት ጉዳይ ምን መሰለሽ? አንደኛ የአንድን አገር የፕሬስ ሁኔታ ለማየት ከፈለግሽ ወደ አወቃቀሩ ነው የምትሄጂው፡፡ አወቃቀሩ አሀዳዊ ነው ወይስ ብዝሀነትን ያስተናገደ ነው የሚለውንም ታያለሽ፡፡ በእኔ እይታ ከአፄ ኃይለሥላሴ እስከ ኮሎኔል መንግስቱና በአሁኑም ስርዓት ስትመጪ አወቃቀሩ አሀዳዊ ነው፣ አንድ ወጥና በአንድ አካል የሚታዘዝ ነው፡፡
ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ የሚሰማው ዜና ከአንድ ምንጭ የሚቀዳ ነው፡፡ ሁሉንም በሞኖፖል የያዘ ነው፡፡  ይሄ “Univocal” ይባላል፡፡ “Multivocal” የሚባለው ደግሞ ብዙ ውድድር ያለበት፣ በአማራጭ የተሞላ ዜና እና የዜና ምንጭ ያለበት ነው፡፡ አሜሪካ ስትሄጂ CNN አለ፣ ABC አለ፣ ሌሎችም መዓት የዜና አውታሮች አሉ፡፡ እዚህ ይህ አይነት አማራጭ የለም፣ ይመጋገባሉ እንጂ፡፡
ይመጋገባሉ ሲሉ እንዴት ነው?
ለምሳሌ የትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ወሬ ነው የሚያወራው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት አወቃቀሩ ተመሳሳይና የሚታዘዘው በአንድ አካል ስለሆነ ነው፡፡ ማንም ሰው ቴሌቪዥን ጣቢያ በግሉ የመክፈት መብትም የለውም፡፡ እንዲህም ሆኖ አሁን ትንሽ ለቀቅ ተደርጎ በጥቂቱም ቢሆን ትችትም እየተፃፈ ነው፣ ይህን አልካድኩም፡፡ “Freedom of speech” እና “Freedom of expression” ይለያል ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡
እስቲ የሁለቱን ልዩነት ያብራሩልኝ?
ይኸውልሽ “Freedom of speech” ብዙ ነገርን ያካትታል፡፡ ለምሳሌ የመሰብሰብን፣ ማህበራት የማቋቋም፣ ለተለያየ የመረጃ ነፃነት እድል የማግኘትን (“exposure” የሚለው ይገልፀዋል) ----- ያካትታል፡፡ በተለያየ አይነት መንገድ መረጃ ክፍት ሆኖና ተፈቅዶለት እንዲያገኝ እድል የሚሰጥ ነው - “Freedom of speech”  ማህበራትን ማቋቋምና የመሰብሰብ ነፃነትም በጣም ጠቃሚ ነገሮች ናቸው፡፡ “Freedom of expression” ደግሞ መናገርን (የአንደበትን) ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡ ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈቀዳል ግን ህዝቡ መረጃ ለማግኘት አማራጮቹ አልሰፉለትም ወይም ህዝቡ ለተለያየ መረጃ “exposed” አይደለም፡፡ ይሄ ነው ልዩነታቸው፡፡ ዋናው ልዩነቱ “Freedom of speech” የሚባለው ነገር ካለ፣ የመረጃ ስብጥሩ ነፃ ነው፡፡ ዜጎች የፈለጉትን መረጃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
እስቲ ለ “Freedom of speech” ማሳያ የሚሆን ምሳሌ ይስጡኝ?
በጣም ጥሩ! ለምሳሌ የአባይ ግድብን ሁኔታ ውሰጂ ፡፡ መንግስት የግድቡ 30 በመቶ ተሰርቷል  አለ፡፡ በቃ! እኛ ይህንን ይዘን ነው ቁጭ ያልነው፡፡ አንቺም ስትፅፊ የሚመለከተው አካል የነገረሽን ነው። አማራጭ የመረጃ ምንጭ ቢኖር እኮ 40 በመቶም 45 በመቶም ሊሆን ይችላል የተሰራው፡፡ አሊያም 15 በመቶም 10 በመቶም ሊሆን ይችላል፡፡ ዜጋው የመንግስት አካል የነገረውን እንጂ ሌላ አያውቅም፡፡ አንድ ግብፃዊ ግን እጅግ በርካታ የሬድዮ፣ የጋዜጣና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስላሉት፣ ስለ አባይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ በብዙ እጥፍ የበለጠና የተሻለ መረጃ የማግኘት እድል አለው፡፡ ይሄ እንግዲህ ነፃ የመረጃ ምንጭ (Freedom of speech) ምን ማለት እንደሆነ ያሳያል፡፡ የፖለቲካ ፈላስፋዎች እንደሚሉት፣ የዜና አውታሩ የመረጃ ምንጩ በሞኖፖል ከተያዘ፣የህዝቡ አንደበት መናገሩ (Freedom of expression) ጥቅም የለውም፣ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውም ይሄው ነው፡፡  
አሁን ያለው ስርዓት (መንግሥት) ራሱ ህግ አውጭ ራሱ ህግ ተርጓሚ ነው፣ ይህ ትክክል አይደለም ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? ህግ አውጭና ተርጓሚው መሆን ያለበትስ ማን ነው?
ዋነው የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ይሄ ነው። “Separation of Power” የሚለው አስተሳሰብ የመጣው ለአንድ መቶ ዓመት ህግንና ነጻነትን በሚመለከት በተነሳው ጥያቄ ዙሪያ ነው፡፡ ይህንንም ለመረዳት መካከለኛው ዘመን ወደ ነበረው የሕግና የሥነ-መለኮት ፍልስፍና እንሂድ፡፡ በዚያን ጊዜ “ህግ የሚገኝ እንጂ የሚረቀቅ አይደለም” የሚለው አስተሳሰብ በሰፊው ተንሰራፍቶ ነበር፡፡
ማነው የሚፅፈው? ማነው የሚያረቅቀው?
በዚያን ወቅት ከላይ በጥቂቱ እንዳልኩት፣ መንግስት ህግ የሚያገኝ አካል እንጂ አርቃቂ አይደለም ብለው ያምኑ ነበር፡፡
እኮ ከየት ነው መንግስት ህግ የሚያገኘው?
ጥሩ ጥያቄ ነው! ከተፈጥሮ ነው ህግ የሚገኘው። ህገ-ተፈጥሮ (Natural Law) ይባላል፡፡ ከዚያ ነው የሚገኘው፡፡ በ15ኛውና በ16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ መንግስት ትልቅ እየሆነ እየተስፋፋ ሲመጣ ህግ ማውጣት ግድ ሆነ፡፡ ሆኖም ግን የተወሰነው የአውሮፓ የማኅበረሰብ ክፍል “በፍፁም ህግ ልታወጡ አትችሉም፡፡ ራሳችሁ ህግ አውጥታችሁ ራሳችሁ ልትዳኙን አትችሉም፣ ነጻነታችን  አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል ክርክር ተነሳ፡፡
ከተፈጥሮ በግልፅ ይገኛሉ የሚባሉት ህጎች ምንድናቸው?
ጥሩ! ሰው መግደል አይፈቀድም - ይሄ ተፈጥሯዊ ህግ ነው፡፡ ሰው የመናገር መብት አለው፡፡ ያጠፋ ሰው ይቀጣል፡፡ የእኛም ፍትሀ-ነገስት ላይ ያሉት እኮ ከተፈጥሮ ህግ የተገኙት ናቸው፡፡ ህገ-ተፈጥሮ ለምሳሌ ወላጅ ልጁን ማሳደግ አለበት፡፡ ልጅ አባቱን አይመታም፡፡ በሰው ልቦና ላይ የተቀረፁ የተፈጥሮ ህጎች እኮ አሉ፡፡ በኋላ የግድ ህግ ማውጣቱ ሲመጣ፣ ህግ አውጭውና ህግ ተርጓሚው ይለያይ ተባለ፡፡ የእነዚህ አካላት መለያየት ግድ የሆነው ከመቶ አመት ጭቅጭቅ በኋላ ነው፡፡ እንግዲህ ከላይ እንዳልኩሽ የሴፓሬሽን ኦፍ ፓወር የመጣው ህግ አውጪውንና ህግ ተርጓሚውን በመለየት ለተቃውሞው ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡
ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት ማለት ለምሳሌ አበራሽ በአበራሽ ጉዳይ ላይ ራሷ ወሳኝ ናት አይደለችም? ነው ጥያቄው፡፡ መልሱ መሆን የለበትም ነው፡፡ የህግ የበላይነት ማለት ሌላ ሶስተኛ አካል በተነሳው ጉዳይ ላይ ነፃ ሆኖ ይዳኝ ማለት ነው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው ይዳኙ ነበር። ደርግ በራሱ ጉዳይ ላይ ይዳኝ ነበር፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፣አሁን ኢህአዴግ በራሱ ጉዳይ ላይ ይዳኛል ወይንስ አይዳኝም ብለሽ ብትጠይቂ፤ በእኔ እምነት ይዳኛል፣ ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም። ህጉን ተመርኩዞ ነፃ ሆኖ የሚዳኝ ዳኛ የለንም እያልኩሽ ነው፡፡ ኢህአዴግ ጋዜጦችንና ሚዲያውን እንደያዘ ሁሉ፣ፍርድ ቤቶችንም ወጥሮ ይዟል፡፡
ፍርድ ቤቶቹ ነፃ አይደሉም እያሉኝ ነው?
ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነፃ ሆነው እየሰሩ አይደለም፡፡ ትቀልጃለሽ እንዴ? ከብርቱካን ሚዴቅሳ ወዲህ በዚህች አገር ፍ/ቤት ላይ ማን ነፃ ሆኖ ትክክለኛ ፍትህ ሰጠና ነው፡፡
እስቲ ለዚህ ስጋት እንደ ማሳያ የሚያቀርቡት ካለ ይግለፁልኝ?    
ለዚህ ማሳያ ላቅርብልሽ ---- የፀረ - ሽብር ህጉን 90 በመቶውን ያመጣነው ከውጭ ቀድተን ነው ይላሉ፡፡
ከውጭ  መቀዳቱ ምን ክፋት አለው ይላሉ?
ክፋት አለው ያልኩት እኮ እኔ አይደለሁም! እነሱው የቀዱባቸው አሜሪካኖችና እንግሊዞች ልክ አይደላችሁም በሚል ወጥረው ይዘዋቸዋል፡፡ ለምን ይመስልሻል? ዋናው ነገር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ የእነሱ ህግ በጣም ስለሚያምር ለጥቁር አይገባውም ብለው ይመስልሻል? አይደለም! “በአገራችሁ ነፃ የሆነ ዳኝነት ስለሌለ ሰው ይጎዳል፣ መጠበቂያ የሌለው ጠብመንጃ ነው” ነው ያሏቸው፡፡ “እኛ እኮ ይህን ህግ ያወጣነው መጠበቂያ ስላለን ነው፡፡ ነፃ ዳኝነት በሌለበት ይህን ህግ እንዴት ሥራ ላይ ታውላላችሁ” ነው ያሏቸው፡፡ ማሳያዬ ይሄ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ማሳያ ትፈልጊያለሽ እንዴ?
ዶ/ር ዳኛቸው “መንግስትና ዩኒቨርሲቲውን ይዘልፋሉ፡፡ ነገር ግን በዩኒቨርሲቲው እያስተማሩ ደሞዝ ያገኛሉ”የሚል ትችት የሚሰነዝሩ አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?
ይሄ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው! ይገርምሻል እዚህ አስተሳሰብ ላይም ችግር አለ፡፡ “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” በሚል ርዕስ የዛሬ መቶ ዓመት በገ/ህይወት ባይከዳኝ የተፃፈ መፅሀፍ አለ፡፡ ፀሐፊው ለአፄ ምኒልክ ምክር ያቀረቡበት አለ፡፡ በመንግስት ላይ አንድ ግድፈት ያየሁት የመንግስት እና የንጉሱ ንብረት ያልተለየ መሆኑ ላይ ነው ብለዋል - ገ/ህይወት ባይከዳኝ፡፡ የደጃዝማቾቹ ንብረትና የአገሬው ህዝብ ንብረት በትክክል መለየት አለበት ነው ያሉት፡፡ እነዚህ ደጃዝማቾችና ሌሎች ሹማምንት በደሞዝ መተዳደር አለባቸው ብለዋል፡፡     
የመንግስት ንብረትና የንጉሡ ንብረት መለየት አለበት እኔ አሁንም የምፈራው፣ የፓርቲ ንብረትና የህዝቡ ንብረት አልተለየም ብዬ ነው፡፡ ኢህአዴጎቹ እኛ ቀጥረነው እኛው ስራ ሰጥተነው ይላሉ፡፡ አንድ ነገር ልንገርሽ - አፄ ኃይለ ሥላሴና ራስ ካሳ ከዝምድናቸው ባሻገር የቅርብ ወዳጆች ናቸው፡፡ ቀልድ ይቀላለዳሉ፡፡ ሁለት ታሪክ ነው የማወራሽ። በጅሮንድ ተክለ ሐዋሪያት ተክለማሪያም ከተፈሪ ጋር ተጣልተው ራስ ካሳ ጋር ይሄዱና “ስራ ስጡኝ” ይሏቸዋል፡፡ ራስ ካሳ ግን “አንተ የተፈሪ አሽከር ስለሆንክ ስራ አልሰጥህም” ይሏቸዋል፡፡ ራስ ካሳ “እርሶ ምን ነካዎት? እኔ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰራተኛ እንጂ የተፈሪ አሽከር አይደለሁም” ይላሉ ተ/ሐዋሪያት፡፡
“እኔ አሁን ስራ ለቅቄያለሁ-- ለምንስ አሽከር ይሉኛል” ሲሉ ራስ ካሳን ይሞግታሉ፡፡ አየሽ መንግሥትና ንጉሥን ራስ ካሣ መለየት አልቻሉም። ኢህአዴጎችም ከዚህ አስተሳሰብ ስላልተላቀቁ ነው “እኛ ስራ ሰጥተነው፣ እኛ ቤት ሰጥተነው፣ እኛ ደሞዝ እየከፈልነው እኛኑ ይሳደባል ይዘልፋል” የሚሉት፡፡ እኔ ግን ስራ የሰጠችኝ አገሬ ኢትዮጵያ እንጂ እነሱ አይደሉም፡፡
ኢትዮጵያ “እስከዛሬ በክፉና በደግ ጊዜ ሳናይህ እንዴት መጣህ አላለችም፣ እንኳን ደህና መጣህልኝ ልጄ” ብላ ነው ስራ የሰጠችኝ፤ይህንን አስረግጬ እነግርሻለሁ፡፡ ስለዚህ ስራ የሰጠኝና ደሞዝ የሚከፍለኝ ማን እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡
ከዚህ ቀደም ዶ/ር ዳኛቸው የብአዴን አባል ናቸው የሚል ነገር ተወርቶ በነበረበት ጊዜ ስጠይቅዎት “እንኳን የብአዴን የምወደው የኢህአፓ አባልም አልሆንኩም የየትኛውም ፓርቲ አባል የማልሆነው በአካዳሚክ ስራዬ ላይ ነፃነት እንዳላጣ ነው” ብለውኝ ነበር፡፡ ያስታውሳሉ?
በደንብ አስታውሳለሁ እንጂ!
ታዲያ በአሁኑ ወቅት በየፖለቲካ መድረኮቹ ላይ ፅሁፍ ያቀርባሉ፣ ትችቶችን ይሰነዝራሉ፡፡ ይሄ ነገር  በስራዎ ላይስ ተፅዕኖ የለውም?
በጣም ጥሩ! ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ጋር በፍፁም ግንኙነት የለውም፡፡ በአካዳሚክ ስራዬም ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም፡፡ እንዴት የሚል ጥያቄ ካነሳሽ ደግሞ፤ እኔ እንደ አንድ ሲቪል ግለሰብ ነው እየተቸሁ ያለሁት፡፡ ሁለት አይነት ምክንያታዊነት አለ- አንደኛው ግለሰባዊ ምክንያታዊነት ይባላል፤ ሁለተኛው ደግሞ ማኅበረሰባዊ ምክንያታዊነት (public reason) ይባላል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ማህበረሰባዊ ምክንያታዊነቴን ተጠቅሜም እየተቸሁ ነው፡፡ ሁለቱ አብረው ይሄዳሉ፡፡ እንደግለሰብ ደግሞ እያስተማርኩ ነው፡፡ በሙያዬም እያገለገልኩ ነው ማለት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች በፍፁም አይጋጩም፡፡ ምናልባት ሊጋጭ የሚችለው የፓርቲ አባል የሆንኩ እንደሆነ ነው፡፡
የፓርቲ አባል ቢሆኑ የአካዳሚክ ስራውና የፓርቲ አባልነቱ የሚጋጩበትን መንገድ ሊገልፁልኝ ይችላሉ?
ማስተማርም ሆነ የፖለቲካ ስራ የሙሉ ሰዓት ስራ እንጂ የትርፍ ጊዜ ስራ ስላልሆኑ ሁለቱም ራሳቸውን ችለው መሰራት ያለባቸው ነገሮች ናቸው፤ ይጋጫሉ የምልሽ፡፡
ግን እኮ እንደ እርሶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲ የሚስተምሩ ሌሎች ምሁራን በአንድ በኩል እያስተማሩ ወዲህ ደግሞ ፓርቲ እየመሩ ነው፡፡ እንዴት ያዩታል?
 እኔ በዚህ በፍፁም አልስማማም! ይሄ የራሴ አቋም ነው፡፡ በእኔ እምነት እነዚህን ስራዎች በአንዴ ስትሰሪ ከሁለቱ አንዱ ይጎዳል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ከበደችና ዘነበችን በአንዴ እወዳለሁ የሚለው ጉዳይ የማያስኬድ ፍልስፍና ነው፡፡ ከከበደችና ከዘነበች በጣም የምወደውን መምረጥ አለብኝ፡፡ አለበለዚያ አንዷን መጉዳቴ ግልፅ ነው፡፡ ይሄ ማለት ወይ ትምህርቱ አሊያም ፖለቲካው ጉዳት ይደርስበታል ማለት ነው፡፡ ይህ የእኔ እምነት ነው። በበኩሌ በዩኒቨርሲቲው ለመቆየት ካልቻልኩ ወደ አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ እቀላቀላለሁ፡፡ እያስተማርኩ ግን የየትኛውም ፓርቲ አባል መሆን አልፈልግም፡፡
በአንድ ወቅት ለሰማያዊ ፓርቲ ንግግር እንዲያደርጉ በተጋበዙበት ወቅት ከአንድ የጋዜጣ አዘጋጅ ጋር ተጋጭተው ስለነበር የዛ ጋዜጣ መቅረፀ ድምፅ ካልተነሳ ንግግር አላደርግም ማለትዎን ብዙዎች አልወደዱትም፡፡ ዶ/ሩ ምሁር ሆነው ቂምን ለትውልድ ያስተምራሉ በሚል ተተችተዋልና ምን ይላሉ?
አንድና አንድ ነገር ልንገርሽ፡፡ አንድ ሰው ድምፄን አልቀዳም የማለት መብት አለው፡፡ ምሳሌ ልጥቀስልሽ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል በቅርቡ 50ኛ ዓመቱን ሲያከብር፤ ፕሮፌሰር ባህሩ ድምጽ መቅረጽ አትችሉም ብለው መቅረፀ-ድምፅ አስነስተዋል፡፡
እንደዚህ ኣይነት በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የእኔ ምን አዲስ ነገር አለውና ነው? እኔ በጎን እኮ አይደለም ይሄ ጋዜጣ እየሰደበኝ ስለሆነ መቀዳት አልፈልግም ያልኩት፡፡ ማንስ ቢሆን መሰደብ ይፈልጋል እንዴ፡፡ አሁን ያልኩሽ ጋዜጣ ወደፊትም ሊቀዳኝ አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ሰዎች በዚህ ነገር ደስተኛ አይደሉም ላልሽው፤ እኔ እንዳንቺ እርግጠኛ ሆኜ ባልናገርም፤ ጓደኞቼ እንደነገሩኝ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አስተያየት ሰጪዎች በማህበረሰብ ሚዲያው በሰጡት አስተያየት፤ በዚህ ጋዜጣ ያለመቀዳት መብት እንዳለኝ ብቻ ሳይሆን ዘለፋቸው ከመስመር የወጣ መሆኑንም መስክረዋል፡፡ ቂም ለምትይው ቂመኛ አይደለሁም፡፡
እኔ እስከምረዳው ድረስ አንድ ሰው፤ በማስታወስና በቂም መካከል ያለውን ልዩነት በቅጡ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡ በመሆኑም ማስታወስ ማለት ማቄም ማለት አይደለም፡፡ ስድስት ወርና አንድ ዓመት ያልሞላውን ጉዳይ ማስታወስህ ቂመኛ ያደርግሀል የሚለው አገላለጽ አግባብ አይደለም። አልቀበለውምም፡፡ ከዚህ በፊትም እንዳልኩት ሰዎች እንደዚህ ነህ፤ እንደዚያ ነህ ባሉኝ ቁጥር ራሴን ለመከላከል ምላሽ መስጠቱ ተገቢነቱን አላምንበትም፡፡

ተቃዋሚዎች የጋራ ፕላኑን ተቃወሙ
ዕቅዱ የአዲስ አበባን የመሬት ችግር ለመፍታት እንጂ ለልማት አይደለም - (ኦፌኮ)
     አዲስ አበባንና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን በልማት ለማስተሳሰር ላለፉት ሁለት ዓመታት ጥናት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፤ የተቀናጀ የጋራ ልማቱን ለመተግበር የተዘጋጀው የጋራ ማስተር ፕላን ባለፈው ሳምንት በአዳማ በተካሄደ የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ ለውይይት ቀርቦ ነበር፡፡
የአዲስ አበባንና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን የ10 ዓመትና 25 ዓመት የልማት ዕቅዶች የያዘው የጋራ ማስተር ፕላን የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጥያቄዎችና ስጋቶችን የቀሰቀሰ ሲሆን ህገ መንግስታዊ ጥያቄም አስነስቷል፡፡
የኦሮሚያ ልዩ ዞን እስካሁን የአዲስ አበባ  ቆሻሻ መጣያ ሆኖ እንደቆየ የጠቀሱት አንድ የውይይቱ ተሳታፊ፤ አንድ ከተማ ዕቅድና ፕላን ይዞ ሲነሳ የራሱ ፖሊሲ አይኖረውም ወይ?” ሲሉ ጠይቀው “አንዱ ተቀባይ አንዱ ሰጪ ሆኖ እስከመቼ ይዘለቃል? ብለዋል፡፡ ልዩ ዞኑ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደመኖሩ ጨፌ ኦሮሚያ በዞኑ ላይ የመወሰን ስልጣን አለው የገለፁት እኚሁ ተናጋሪ፤ ጨፌ ኦሮምያ በጉዳዩ ላይ ሳይወያይና ሳይወስን ወደ ተግባር ከተገባ ስልጣን መጋፋት አይሆንም ወይ?” በማለት አስረግጠው ጠይቀዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሠጪ በበኩላቸው፤ “አገሪቱ የምትተዳደረው በፌደራሊዝም ስርዓት ነው፤ በመጀመሪያ ህዝቡ መወያየት ነበረበት፡፡ ጥናቱ ከተጀመረ ሁለት ዓመት ቢሆነውም ጉዳዩ ሳይነገር ቆይቶ አሁን ነው የተነሳው፡፡ ህገመንግስቱ በፖሊሲም ሆነ በፕሮጀክት ቀረፃው ላይ ህዝቡ መሳተፍ አለበት ይላል፤ ነገር ግን ተግባራዊ አልሆነም፡፡” ሲሉ ተችተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሰየሙት አመራሮች በበኩላቸው፤ የጋራ ማስተር ፕላኑ ከሌሎች ያደጉ ሀገሮች የተኮረጀ መሆኑን ጠቁመው፤ እነ አሜሪካ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ በዚህ ሁኔታ ነው ያደጉት ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፤ “ሌሎች አገሮች ተሞክሮዎች መኮረጅ መልካም ቢሆንም ስንኮርጅ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እየተገናዘበ መሆን እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ “ይሄ በፊንፊኔ ዙሪያ ብቻ ያለ ኦሮሞ ጉዳይ ሳይሆን የእያንዳንዱ ኦሮሞ ጉዳይ ነው፤ ሁሉም ሊወያይበት ይገባል፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡  የጋራ ፕላኑ አርሶ አደሩን ለስደትና ለሥራ አጥነት ይገፋል ለሚለው የተሳታፊዎቹ አስተያየት የመድረኩ መሪዎች ሲመልሱ፤ በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ዘላቂ ጥናቶች እንዳሉ ጠቁመው “አርሶ አደሩ ተገቢው ካሣ እየተከፈለው ተደራጅቶ እንዲሰራ እገዛ ይደረግለታል” ብለዋል፡፡ የጋራ ልማት ከጋራ ችግር ነው የሚነሣው ያሉት አወያዮቹ፤ የኦሮምያ ልዩ ዞን ልዩ ተጠቃሚ ይሆናል የሚለውን የህገመንግስቱን ድንጋጌ የተቀናጀው የጋራ ፕላን ተግባራዊ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
የጋራ ማስተር ፕላኑን አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ ማብራሪያ የሰጡት የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ም/ስራ አስኪያጅ አቶ ለአለም አዲስ የተዘጋጀው ማስተር ፕላን የኦሮምያ ልዩ ዞን ከተሞችን ወደ አዲስ አበባ እንዲጠቃለሉ የሚያደርግ ሣይሆን በመሠረተ ልማት ተሳስረው በጋራ የሚያደርጉበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ውሃ፣ የማገዶ እንጨት፣ የከብት መኖ፣ የወተት አቅርቦት፣ አትክልት የመሣሰሉትን በዙሪያዋ ካሉ ከተሞች እንደምታገኝ የገለፁት አቶ ለአለም፤ በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች በበኩላቸው የስራና የትምህርት ዕድል፣ የትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች ከአዲስ አበባ ያገኛሉ ብለዋል፡፡
ከ25 አመት በኋላ የዘመነች ከተማን ለመፍጠር ያስችላል የተባለው ማስተር ፕላን በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ያሰፍናል ተብሏል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዱላዚዝ አህመድ፤ የጋራ ማስተር ፕላኑ ሁለቱን ክልሎች በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ አስተዳደራቸው በበጐ እንደሚቀበለው ገልፀዋል፡፡    
በሌላ በኩል የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን የተቃወሙ ሲሆን የመድረክ ግንባር አባል የሆነው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ ፕላኑ ተግባራዊ እንዳይሆን ጠይቋል፡፡ “የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችንና ወረዳዎችን ከትልቋ ከተማ ፊንፊኔ ጋር በልማት ለማስተሳሰር በሚል ሰበብ ብቻ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በሊዝ የሚሸጠውን የመሬት አቅርቦት ለማሟላት ነው” ብሏል - ፓርቲው፡፡
የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቶ በቀለ ነጋ በሰጡት ማብራሪያ፤ አዲስ አበባን ከኦሮምያ ልዩ ዞን ጋር ለማስተሳሰር የሚደረገው ሩጫ የህገ መንግስት ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ይላሉ፡፡ “ክልሎች የራሳቸው የሆነ ዳር ድንበር አላቸው፤ የራሳቸው አስተዳደርም አላቸው፤ አዲስ አበባ ደግሞ በኦሮሚያ ስር ስላልሆነች ማስተር ፕላን መሰራት ካለበት በኦሮሚያ ክልል ባለቤትነት ነው” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ እቅዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የመሬት ችግር ለመፍታት እንጂ ለልማት አይደለም የሚሉት አቶ በቀለ፤ አዲስ አበባ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን በስፋት የምታገኘው ከኦሮሚያ መሆኑን ጠቅሰው የኦሮሚያ ልዩ ዞን በልማት መተሳሰሩ አሁንም የተጠቃሚነት ሚዛኑን ለአዲስ አበባ እንዲያደላ የሚያደርግና በአካባቢው ያሉ ኦሮሞዎችን ጥቅም የሚነካ ነው ብለዋል፡፡
የጋራ ማስተር ፕላኑ ከኦሮሚያ መሬት ብቻ አይደለም የሚነጥቀው የሚሉት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ፤ በአካባቢው ያሉ ኦሮሞዎች የቋንቋና የማንነት ጉዳይም ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ “የመሬት ነጠቃ ብቻ ሳይሆን በግልፅ ህገ መንግስቱን በጣሰ መልኩ የማንነት ነጠቃም ነው” ይላሉ አቶ በቀለ፡፡ “አዲስ አበባ የኦሮምያ እምብርት ናት” የሚለው የአመታት ጥያቄ ባልተመለሰበት ሁኔታ፣ የማስፋፊያ እቅዱ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ አሳሳቢ ነው ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ አዲስ አበባ በአሁን ወቅት የመብራት፣ የውሃና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ከኦሮሚያ ልዩ ዞን  እንደምታገኝ ጠቅሰው፤ በአንፃሩ ከጥቂት ዓመታት በፊት አሣ ይጠመድባቸው የነበሩ አቃቂ ወንዝን የመሳሰሉ መዲናዋን የሚያቋርጡ ወንዞች፣ በከተማዋ ፍሳሾች ተመርዘው የኦሮሚያ ልዩ ዞን
ነዋሪዎች ላይ አደጋ እያስከተሉ ነው ብለዋል - የተመረዘውን ውሃ ለመጠጥ እና ለከብቶቻቸው እንዲሁም ለመስኖ እርሻቸው እንዲጠቀሙ  መገደዳቸውን በመጠቆም፡፡ “ህዝባችን በመርዝ የተበከለ ውሃ እየጠጣ ነው” ሲሉ የሚያማርሩት አቶ በቀለ፤ “የአካባቢው የኦሮሚያ ነዋሪዎች ጥቅማቸው ተነክቷል፤ የመኖር ህልውናቸውም አደጋ ላይ ወድቋል የምንለው በዚህ መነሻ ነው” ብለዋል፡፡  ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ የነበሩ የገበሬ ማህበራት መሬታቸው እየተነጠቀ ያለ ቅድመ ሁኔታና ግንዛቤ መተዳደሪያቸውን ከግብርና ወደ ሌላ መስክ እንዲቀይሩ መገደዳቸውን ያስታወሱት አስተያየት ሰጪው፤ በዚህ የተነሣ ከመሬቱ የተፈናቀለው ገበሬ በችግር ላይ ነው ብለዋል፡፡ “እኛ ጥያቄያችን የአዲስ አበባ ድንበር የት ላይ ነው የሚቆመው የሚለው ነው” ያሉት አቶ በቀለ፤ መንግስትን በተለያዩ አግባቦች እንጠይቃለን ብለዋል፡፡  የመድረክ ስራ አፈፃፀም አባል አቶ ገብሩ ገ/ማርያም በበኩላቸው፤ የፌደራል ስርአቱ ሲዋቀር ሁሉም ክልሎች የማይጣስ የማይገሰስ ድንበር እንደሚኖራቸው መደንገጉን አስታውሰው፤ አሁን በመንግስት የተያዘው አቅጣጫ በቀጥታ ይህን ድንጋጌ መጣስ ነው፣ ጥሰቱ እንዲቆም መግለጫ ከማውጣት ባሻገር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
በሽግግር መንግስቱ ወቅት በህገመንግስት ማርቀቅ ተግባር ላይ ጉልህ ሚና የነበራቸው የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትና የታሪክ ምሁር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ አወዛጋቢውን የአዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊ ዳራ ያስታውሳሉ፡፡ በደርግ ጊዜ የሃገሪቱን መዲና ሰፊና ትልቅ ለማድረግ ታስቦ፣ በአራቱም ማዕዘናት የማስፋፊያ እቅዶች ነበሩ የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ ድንበሩ ናዝሬት፣ ወልቂጤ፣ አምቦ ድረስ እንዲሆን ታስቦ ነበር ይላሉ፡፡ “ደርግ ከወደቀ በኋላና በሽግግሩ ጊዜ አዲስ ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ አሁን ያለው ድንበር እንዲሆን ተወሰነ፣ አዲስ አበባና ኦሮሚያም በግልፅ ድንበራቸው ይካለል ተባለ” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ የተባለው የማካለል ስራ በግልፅ ስለመፈፀሙ መረጃ እንደሌላቸውና አሁን የተፈጠረው ቅሬታም የዚሁ መነሻም ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡  
አዲስ አበባ በኦሮሞ ብሄርተኞች የባለቤትነት ጥያቄ የሚነሳባት ከተማ ነች የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ “በሽግግሩ ወቅትም ሆነ በምርጫ 97 ጊዜ ‹በአፄ ምኒልክ በሃይል የተወረረች የኦሮሞዎች ግዛት ነች” የሚል ጉዳይ ተነስቶ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ጥያቄ መቅረቡንና ብዙ ንትርክ ማስነሳቱን ጠቁመው፤ ሆኖም እስካሁን ጥያቄው መልስ ስለማግኘቱ እርግጠኛ አይደለሁም ብለዋል፡፡ “አሁን ላይ የሚነሳው ጥያቄ በልማት የመተሳሰር ጉዳይ ብቻ ከሆነ ቀድሞውንም ተሳስረዋል፣ የመሬት ሽሚያ ተስፋፍቶ ለገጣፎን በመሳሰሉ አካባቢዎች የኦሮሚያ አርሶ አደሮች መሬት ተወስዷል፣ አሁን እየተደረገ ያለው ያንን አጠናክሮ የሚያስቀጥል ደባ ነው” የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ሩ፤ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ድንጋጌ መሰረት የኦሮምያ ልዩ ጥቅም ባይጠበቅም በመሰረተ ልማት መተሳሰር የሚለው አጀንዳ ግን በሌላው አለምም የሚሰራበት በመሆኑ የሚያስኬድ ነው ብለዋል፡፡
በህገ መንግስቱ አንቀፅ 49(5) “የኦሮሚያ ክልል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉ ጉዳዮችን በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” የሚል ድንጋጌ መስፈሩን የጠቀሱት ዶ/ር ነጋሶ፤ እስካሁን ግን ኦሮሚያ እንኳንስ ጥቅም ሊያገኝ መሬቱን እየተነጠቀ ነው ብለዋል፡፡ “የኦሮሚያ ልዩ ዞን ለግንባታ የሚውሉ ድንጋይና ጠጠር የመሳሰሉ የተፈጥሮ ሃብቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን ለአዲስ አበባ ገባሪ ሆኗል” ሲሉም ተችተዋል፡፡ በአንድ ወቅት የኦሮምያ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ያለውን ቅሬታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ ማስታወቁን የሚያስታውሱት ዶ/ር ነጋሶ፤ ምላሽ ስለማግኘቱ ግን መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ባሉበት ሁኔታ የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላን ተግባራዊ ሊደረግ መታሰቡ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ አሰራሩ ግን አዲስ እንዳልሆነና የሰለጠኑ ሃገራትም አስተዳደራዊ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ሣይገቡ የጋራ መሰረተ ልማቶችን በጋራ አቅደው እንዲሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የተቀናጀ የጋራ ፕላኑ ምን ይዟል?
የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላኑ የ10 ዓመት እና የ25 ዓመት ግቦችን ያስቀመጠ ሲሆን በሁለቱ ተጎራባቾች መካከል በሚፈጠረው የመሰረተ ልማት ትስስሮች ከ10 እና ከ25 ዓመት በኋላ አዲስ አበባ የምትደርስበትን ደረጃ ይገልፃል፡፡ ከ10 ዓመት በኋላ አዲስ አበባን የአለማቀፍ ጉባኤዎችና ድርጅቶች መቀመጫ፣ ከአፍሪካ 2 ተመራጭ ከተሞች አንዷ፣ ዘላቂ አለማቀፍ የዲፕሎማቲክ መዲና እንዲሁም ከ10 ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ አንዷ የማድረግ ዕቅድ ያስቀመጠው የጋራ ፕላኑ፤ ከ25 አመት በኋላ ደግሞ ከ5ቱ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ አንዷ የማድረግ ግብ አስቀምጧል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች አደረጃጀት ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ አለመሆናቸውን የሚጠቁመው የጋራ ፕላኑ፤ ከተማዋን በ15 ክፍለ ከተሞችና በ137 ወረዳዎች ለመሸንሸን መታቀዱን ያመለክታል፡፡ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የሆኑት ሰበታ፣ ሱሉልታ፣ ለገጣፎ-ለገዳዲ፣ ቡራዩ፣ ገላን-ዱከም ደግሞ ከ8-10 የሚደርሱ ወረዳዎች እንደሚኖራቸው ይገልፃል፡፡
ከ10 እና 25 ዓመታት በኋላ በሁለቱ ትስስሮሽ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የመንገድ ትስስሮሽ፣ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፣ የነዋሪው ኢኮኖሚ፣ የቤቶች ልማት፣ የህዝብ ቁጥሩ፣ የአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም የህንጻ ግንባታዎች ምጣኔ ምን ላይ ሊደርስ እንደሚችል የሚጠቁም ግምታዊ ስሌት በጋራ ፕላኑ እንደተካተተ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ዜና

ድምፃዊ ጎሳዬ “ሃይማኖቱን ቀየረ” በሚል በመገናኛ ብዙሃንና በድረ-ገፆች የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑን ገልፆ መገናኛ ብዙሃኑ ስህተታቸውን ካላስተባበሉ ክስ እንደሚመሰርት በጠበቃው በኩል ለአዲስ አድማስ ገለፀ፡፡
ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ “ሃይማኖቱን ቀይሮ ሙዚቃ በቃኝ በማለት መዝሙር ሊያወጣ ነው” በሚል በዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮና በ “ቃልኪዳን” መጽሔት የተሰራጨው ሃሰተኛ ዘገባ  የድምፃዊውን ስምና ዝና የሚያጠፋ ነው ያሉት ጠበቃው አቶ ጳውሎስ ተሰማ፤ የሚዲያ ተቋማቱ በአስቸኳይ ማስተባበያ እንዲያወጡ ጠይቀው፤ ይህ ካልሆነ ግን ክስ እንደሚመሰረትባቸው አሳስበዋል፡፡
ድምፃዊው ሃይማኖቱን በተመለከተ ለማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን የሰጠው አስተያየትም ሆነ ቃለ ምልልስ የለም ያሉት የአርቲስት ጐሳዬ ጠበቃ፤ የቀረበው ዘገባ የድምፃዊውን አድናቂዎችና የሙዚቃ አፍቃሪዎቹን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳሳነና ያስደነገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ “በዳጊ ምልከታ” በተሰኘ ፕሮግራም፤ ድምፃዊው “ሃይማኖቱን ቀይሮ የመዝሙር ነጠላ ዜማ ሊለቅ ነው፤ ከአርቲስት መሐሙድ አህመድ ጋር በለቀቁት ነጠላ ዜማ የገባውን ቃል አልጠበቀም” የሚል የተሳሳተ ዘገባ መሠራጨቱን ጠበቃው ገልፀዋል፡፡
በሚያዚያ 4/2006 ለንባብ በበቃው “ቃልኪዳን” መጽሔት ላይም “ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ ዘፈን አቁሞ ዘማሪ ሆነ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ “አሁን ዳግመኛ ተወልጃለሁ፤ ጌታ ለዚች ቀን ስለመረጠኝ ክብርና ምስጋና ለናዝሬቱ ኢየሱስ ይገባዋል፤” ብሎ መናገሩንና ሙዚቃ በቃኝ ብሎ ማቆሙን ከፎቶግራፉ ጋር መውጣቱን ጠበቃው ተናግረዋል፡፡
የቀረቡት ዘገባዎች ሃሰተኛ ስለሆኑ መጽሄቱም ሆነ ዛሚ ኤፍ ኤም ሬድዮ ድምፃዊውን እንዲሁም አንባቢና አድማጩን ይቅርታ በመጠየቅ እንዲያስተባብሉ አሳስበዋል፡፡ መገናኛ ብዙሃኑ ይህን የማያደርጉ ከሆነ ግን ክስ በመመስረት የጉዳት ካሳ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡  
“ሃይማኖቱን ቀየረ” የሚለው ወሬ በፈረንጆች ኤፕሪል መጀመሪያ ላይ በፌስ ቡክ እንደተሰራጨ የገለፀው ድምፃዊ ጎሳዬ፤ ትንሽ ቆይቶ እዚያው ፌስ ቡክ ላይ “ኤፕሪል ዘ ፉል ነው” የሚል ነገር እንደወጣ ይናገራል፡፡ ሃሰተኛ የፈጠራ ወሬ መሰራጨቱ ለጊዜው እንዳናደደው የገለፀው ጎሳዬ፤ ወዲያው ግን ለወሬ ጊዜና ቦታ አልሰጥም ብሎ ስራው ላይ ማተኮሩን ተናግሯል፡፡
ከአንጋፋው ድምፃዊ መሃሙድ አህመድ ጋር ባወጡት ነጠላ አልበም የገባውን ቃል አልጠበቀም በሚል የተሰራጨው ወሬ የተሳሳተ ነው ያለው ጎሳዬ፤ አዲስ አልበም ለማውጣት ቀን ከሌት እየሰራ መሆኑንና ቃሉን እንዳላጠፈ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ በቅርቡም ከአዲሱ አልበም ነጠላ ዜማ እንደሚለቅ ጠቁሞ፣ ለክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ መልካም የትንሳኤ በዓል ተመኝቷል- ድምፃዊው፡፡

Published in ዜና

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የማስታወቂያ ሥራን በፈር ቀዳጅነት እንደጀመሩ በሚነገርላቸው በአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ የህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ‹‹ያልመከነ ማንነት›› የተሰኘ  መጽሐፍ ከትናንት በስቲያ በሒልተን ሆቴል ተመርቆ  በገበያ ላይ ዋለ፡፡
በአበበ አያሌው የተዘጋጀው ይኸው መፅሐፍ ፤ የአቶ ውብሸት ወርቃለማሁን ከልጅነት እስከ ዕውቀት የህይወት እርምጃና ስኬት የሚተርክ ነው ተብሏል፡፡ በምርቃት ሥነሥርዓቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ የጥበብ ባለሙያዎች እና የባለታሪኩ ወዳጆች ተገኝተዋል፡፡ በ205 ገፆች የተሰናዳው መፅሐፍ፤ በ94 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

“አንድ ቀን” የቤተሰብ ፊልም በቅርቡ ለተመልካች ይቀርባል

በደራሲ፣ዳይሬክተርና ፕሮዱዩሰር አለማየሁ ታደሰ እንዲሁም በኤክስኪዩቲቭ ፕሮዱዩሰር ማርታ ጌታቸው የተዘጋጀው ‹‹የኔታ›› የተሰኘ ድራማ ኮሜዲ ፊልም፤ የፊታችን ሰኞ በ11 ሰዓት በብሔራዊ ትያትር ይመረቃል፡፡ በፊልሙ ላይ ራሱ አለማየሁ ታደሰን ጨምሮ  ኮሜዲያን ደረጄ ሀይሌ፣ ቃልኪዳን ጥበቡ፣ አስናቀ ንጉሴ፣ማርታ አሰፋ እና ሌሎች ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡
በሌላ በኩል በደራሲና ፕሮዲዩሰር ሜላት ነብዩ እና በዳሬክተር ቢኒያም ወንድይፍራው የተዘጋጀው “አንድ ቀን” የተሰኘ የቤተሰብ ፊልም፣ ሚያዚያ 23 ከቀኑ በ11 ሰዓት በጣይቱ ጃዝ አምባ አዳራሽ  የሚመረቅ ሲሆን በቅርቡ ለተመልካች ይቀርባል ተብሏል፡፡
በሜሊያም መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን በተሠራው በዚህ ፊልም ላይ ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን  የተሳተፉበት ሲሆን ፊልሙን ለማጠናቀቅ አንድ ዓመትና ከ500ሺ ብር በላይ እንደፈጀ አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡

      በዓለም  የአትሌቲክስ  ስፖርት  በረጅም ርቀት፤ በጎዳና ላይ ሩጫ እና በቤት ውስጥ ውድድሮች በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተያዙ የዓለም ሪከርዶች የሚሰበሩበት እድል እየተመናመነ መምጣቱን የተለያዩ ጥናቶች አመለከቱ።  በተለይ በረጅም ርቀት በወንዶች   10ሺ ሜትር እና በሁለቱም ፆታዎች በ5ሺ ሜትር በኢትዮጵያውያን የተመዘገቡት 3 ሪከርዶች በመላው ዓለም ውድድሮቹ ካለመካሄዳቸው በተያያዘ የሪከርድ ሰዓቶቹ በቅርብ ዓመታት መሻሻላቸው ያጠያይቃል ተብሏል፡፡ ቀነኒሳ በቀለ  በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች ያስመዘገባቸው ሁለት የዓለም ሪከርዶች ሳይሰበሩ 10 ዓመታት ያለፏቸው ሲሆን ፤ አትሌቱ በተመሳሳይ ርቀቶች በዓለም ሻምፒዮና የኦሎምፒክ  መድረኮች ያስመዘገባቸውን ሪከርዶች  እንደተቆጣጠረ ነው፡፡  በሌላ በኩል በሴቶች 5ሺ ሜትር ውድድር ጥሩነሽ ዲባባ የያዘችው ክብረወሰን ከተመዘገበ 6 ዓመታት ያለፉት ሲሆን አትሌቷ በረጅም ርቀት በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና ያስመዘገበቻቸው ሪከርድ ሰዓቶች የከፍተኛ ብቃት መለኪያ እንደሆኑ ቀጥለዋል፡፡  በአትሌቲክስ ውድድሮች ሪከርዶችን ካስመዘገቡ የኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል ለ20 አመታት ባሳለፈው የሩጫ ዘመኑ ከ27 በላይ ሪከርዶችን ከ2 ማይል እስከ ማራቶን ባሉ ርቀቶች በማስመዝገብ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከሳምንት በኋላ 41ኛ ዓመቱን የሚይዝ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከትራክ ውጭ በተደረጉ ውድድሮች የተመዘገቡ  ከ3 በላይ የአለም ሪከርዶችን እንደያዘ ነው። በሴቶች 5ሺ ሜትር የትራክ ውድድር በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና ከፍተኛ ውጤት ያላት መሰረት ደፋር በ5 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ያስመዘገበችው ሪከርድ ያልተሰበረ ሲሆን በዓለም የቤት ውስጥ ውድድሮች በ1500 እና በ3ሺ ሜትር የነበሩ ሪከርዶችን ባለፉት 3 እና 4 አመታት እንደተቆጣረች ቆይታ ዘንድሮ የተሰበረባት በኢትዮጵያዊቷ ገንዘቤ ዲባባ ነው፡፡ ገንዘቤ ዲባባ ዘንድሮ በ1500ሜና በ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድሮች እንዲሁም በ2 ማይል ሩጫ ሶስት የዓለም ሪከርዶችን የጨበጠች ሲሆን  በተለይ ሰሞኑን በአይኤኤኤፍ ማረጋገጫ ያገኘችበት የ3ሺ ሜትር ው ሪከርድ በድጋሚ ለመሰበር ቢያንስ 5 አመታትን እንደሚፈጅ ይገለፃል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ ጥናቶችን በመዳሰስ ለመረዳት እንደተቻለው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ከ100 ሜትር እስከ ማራቶን ርቀቶች በየጊዜው ሪከርዶችን በማሳካት የሚሆንላቸው አትሌቶች ከተወሰኑ አገራት የሚገኙ ናቸው፡፡ በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫዎች የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶችን  የውጤት የበላይነትና የሪከርድ ባለቤትነት ላለፉት 20 አመታት የሚቀናቀን ጠፍቷል፡፡ በአጭር ርቀት ውድድሮች ደግሞ የጃማይካ እና የአሜሪካ አትሌቶችን ስኬት የሚስተካከል አልተገኘም።  ከላይ ከተጠቀሱት አራት  አገራት የሚወጡ አትሌቶች በአትሌቲክስ ውድድሮች ያስመዘገቧቸው ሪኮርዶችን የማሻሻሉ እድል በየዓመቱ በ0.5 በመቶ እንደተወሰነ በጉዳዩ ላይ ስፖርትሳይንቲስትስ የተባለ ድረገፅ የሰራው ትንታኔ አመልክቷል፡፡  የላቀ ብቃት፤ የላቀ ፍጥነት እና የላቀ ጥንካሬ በሚለው የኦሎምፒክ መርህ  መሰረት የእነዚህ 4 አገራት ምርጥ አትሌቶች በአትሌቲክስ ስፖርት በሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ብቃት ሊሳካ የሚችለውን የሪከርድ አቅም 99 በመቶ አሟጥጠውታል የሚል ድምዳሜን የስፖርትሳይንቲስት ባለሙያዎች በጥናታቸው አረጋግጠዋል፡፡ በስፖርቱ አለም የ147 ውድድሮች ሪከርድ በሰው ልጅ ብቃት ሊመዘገብ የሚችለው ማጣርያ በ2027 እኤአ  እንደሚያበቃ ያረጋገጡ ጥናቶች አሉ፡፡ አይኤንኤስኢፒ የተባለ እና በፓሪስ ተቀማጭ የሆነ የስፖርት ኢንስቲትዩት በሰራው ጥናት አረጋግጧል።  በአሁኑ ወቅት በስፖርቱ አለም በተለይ በአትሌቲክስ ውድድሮች ሪከርዶችን ለማስመዝገብ እጅግ ወሳኝ ከሆነው ተፈጥሯዊ ክህሎት ባሻገር፤ ለፍጥነት የሚመደቡ አሯሯጮች፤ በቴክኖሎጂ የታገዙ የመሮጫ ጫማዎች፤ ዘመናዊ ህክምናዎች እና መድሃኒቶች፤ እጅግዘመናዊ የስልጠና፤ የአመጋገብ እና የስነልቦና ዝግጅቶች እንዲሁም በስኬት  የሚገኝ ገቢ አስፈላጊ ይሆናሉ፡፡ በዘመናችን በህክምና ረገድ ያሉ አገልግሎቶች እና መድሃኒቶች አትሌቶች ለረጅም ጊዜ እየተወዳደሩ በመቆየት ካላቸው ልምድ ሪከርዶችን የመስበር እድላቸውን ከማስፋቱም በላይ፤ ከጉዳቶች ሙሉ ለሙሉ ለመዳንና ለማገገም በሚኖራቸው እገዛ ስፖርተኞች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል እንደ ጂን ቴራፒ አይነት ዘመናዊ ህክምናዎች ስፖርተኞች በጡንቻዎቻቸው አላግባብ ጉልበት የሚያፈሱበትን ሁኔታ እና ድክመታቸውን በመፈወስ ብቃታቸውን ያግዛል፡፡ በአጠቃላይ የአትሌቶች ብቃት እያደገ ሲቀጥል፤ የቴክኖሎጂ እና የሳይንስ ድጋፍ እየመጠቀ ሲሄድ በርካታ የአትሌቲክስ ሪከርዶች መሻሻላቸው አይቀርም፡፡ በእርግጥ  በዓለም የአትሌቲክስ ውድድሮች በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረክ  የወርቅ ሜዳልያዎችን ከማግኘት በላቀ ሁኔታ እንደከፍተኛ ስኬት የሚቆጠረው ሪከርዶችን ማስመዝገብ ነው፡፡ ለምን ቢባል  የየትኛውንም የአትሌቲክስ ውድድር ሪከርድ ማስመዝገብ በውድድር አይነቱ ያለተቀናቃኝ የበላይነት መያዝ መቻሉን የሚያረጋግጥ ስኬት በመሆኑ ነው፡፡ ሪከርዶች የሩጫ ውድድሮችን የፉክክር ደረጃ ከማሳደጋቸውም በላይ ለተመልካቾች የማይረሳ ልዩ ስሜት በመፍጠርና የስፖርቱን ተወዳጅነት በመጨመር አስተዋፅኦ አላቸው፡፡  ሪከርድ የሚያስመዘገቡ አትሌቶች በተለያዩ የውድድር የቦነስ ሽልማቶች ይጠቀማሉ፡፡ የትጥቅ እና የመሮጫ ጫማዎችን በሚያቀርቡላቸው ስፖንሰሮች ተጨማሪ ክፍያ እና የገቢ እድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚካሄዱ ውድድሮች በቀጥታ ተጋባዥ የሚሆኑበትንም እድል ያገኛሉ፡፡
ባለፉት 15 አመታት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1500 ሜትር እስከ ማራቶን፤ ከ2 እስከ 10 ማይል ፤ በተለያዩ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እንዲሁም ከ2ሺ  እስከ 5ሺ ሜትር በሚደረጉ የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች በአሸናፊነት ፍፁም የበላይነት በማሳየት እና ሪከርዶችን በማስመዝገብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር (አይኤኤኤፍ) በአሁኑ ወቅት በአትሌቲክስ ስፖርቶች 53 ሪከርዶች ተመዝግበዋል፡፡ አይኤኤኤፍ በትራክ ላይ የሚደረጉ የሩጫ ውድድሮችን ሪከርዶች በኦፊሴላዊ ደረጃ መመዝገብ የጀመረው በ1912 እኤአ ሲሆን ቤት ውስጥ የአትሌቲከስ ውድድሮች ደግሞ ከ1987 እኤአ ወዲህ እውቅና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡  በትራክ ላይ የሩጫ ውድድሮች  አይኤኤኤፍ  በወንዶች ከመዘገባቸው ሪከርዶች መካከል አራቱ በሁለቱ የኢትዮጵያ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ እና ኃይሌ ገብረስላሴ ሲያዙ፤ በሴቶች ደግሞ ሶስት ሪከርዶች ሁለቱ በጥሩነሽ ዲባባ እንዲሁም አንደኛው በድሬ ቱኔ እንደተያዙ ናቸው።  በዓለም የቤት  ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች ደግሞ በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ በ5ሺ ሜትር ሪከርድ ሲኖረው፤ በሴቶች ምድብ የተመዘገቡት ሶስት ኢትዮጵያዊ ሪከርዶች ደግሞ ዘንድሮ  በገንዘቤ ዲባባ አማካኝነት በ1500 ሜትር እና በ3ሺ ሜትር የተያዙትና  በመሰረት ደፋር በ5ሺ ሜትር ያስመዘገበችው ናቸው፡፡  ከዚህ በታች በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት የኢትዮጵያ አትሌቶች ያስመዘገቧቸው የዓለም፤ የዓለም ሻምፒዮና እና የኦሎምፒክ እና የልዩ ልዩ ውድድሮች ሪከርዶች ተቀነጫጭበው ቀርበዋል፡፡
ኢትዮጵያዊ የዓለም ሪከርዶች
በ5ሺ ሜትር የትራክ ውድድሮች  በሁለቱም ፆታዎች  የዓለም ሪከርዶች በኢትዮጵያውያን የተያዙ ናቸው፡፡ በወንዶች 5ሺ ሜትር  ከ1884 እኤአ ጀምሮ 37 ሪከርዶች ተመዝግበዋል፡፡ በዚህ የሪከርድ መሻሻል ሂደት 5 ጊዜ ኢትዮጵያን ስድስት ጊዜ ደግሞ ኬንያውያን አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ ከ1994 እስከ 1998 እኤአ ድረስ ለአራት ጊዜያት የ5ሺ ሜትር ሪከርዶችን በማሻሻል ከፍተኛውን ድርሻ የተወጣ አትሌት ነበር፡፡  በ2004 እኤአ በሆላንድ ሄንግሎ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ12 ደቂቃ ከ37.35 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ሪከርድ ግን ላለፉት 10 ዓመታት ሳይሰበር የቆየ ነው፡፡ በራንኒንግ ዎርልድ ጥናታዊ ዘገባ በሰው ልጅ ብቃት በ5ሺ ሜትር ሊመዘገብ የሚችለው ሪከርድ ከ14 ዓመታት በኋላ 12 ደቂቃ ከ09.39 እንዲሁም ከ26 ዓመታት በኋላ ደግሞ 11 ደቂቃ ከ56.19  ሰኮንዶች ሊሆን እንደሚችል ሲገመት 11 ደቂቃ ከ11.61 ሰከንዶች የመጨረሻው የሪከርድ ወሰን ነው፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች 5ሺ ሜትር ከ1922 እኤእ ጀምሮ 27 ጊዜ ሪከርዶች ሲመዘገቡ ከ2004 እኤአ ጀምሮ የተመዘገቡ አራት ክብረወሰኖች በትውልድ ኢትዮጵያዊ በሆኑ አትሌቶች አሳክተዋቸዋል፡፡ በ2004 እኤአ የርቀቱን ክብረወሰን 14 ደቂቃ ከ24.68 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ አስመዝግባ የነበረችው በትውልድ ኢትዮጵያዊ ብትሆንም በዜግነት ለቱርክ የምትሮጠው ኢልቫን አብይ ለገሰ ነበረች፡፡ የኢልቫን አብይ ለገሰን ሪከርድ በ2006 እና በ2007 እኤአ አከታትላ ለመስበር የበቃችው ደግሞ መሰረት ደፋር ናት፡፡ ከእሷ በኋላ ላለፉት 6 ዓመታት ሳይሰበር የቆየውን ሪከርድ በ2007 እኤአ በኖርዌይ ኦስሎ በተካሄደ ውድድር 14 ደቂቃ ከ11.15 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በጥሩነሽ ዲባባ  የተመዘገበው ነው፡፡ በራንኒንግ ዎርልድ ጥናታዊ ዘገባ በሰው ልጅ ብቃት በ5ሺ ሜትር በሴቶች ሊመዘገብ የሚችለው ሪከርድ  ከ14 ዓመታት በኋላ 13 ደቂቃ ከ41.56 ሰከንዶች ከ26 ዓመታት በኋላ ደግሞ 13 ደቂቃ ከ37.25 ሰኮንዶች ሲሆን 12 ደቂቃ ከ33.36 ሰከንዶች የመጨረሻው የሪከርድ ወሰን ነው፡፡
በ10ሺ ሜትር የትራክ ውድድር በወንዶች  ከ1847 እኤአ ጀምሮ 47 ሪከርዶች ሲመዘገቡ የኢትዮጵያ ሁለት አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ እና ኃይሌ ገብረስላሴ ለአምስት ጊዜያት  የሪከርድ ሰዓቶቹን በማሻሻል አስተዋፅኦ ነበራቸው።  በ2005 እኤአ ላይ ቤልጅዬም ብራሰልስ ላይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ያስመዘገበው 26 ደቂቃ ከ17.53 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በርቀቱ ላለፉት 9 አመታት ተይዞ የቆየውን ሪከርድ  አስመዝግቧል፡፡ በራንኒንግ ዎርልድ ጥናታዊ ዘገባ በሰው ልጅ ብቃት በ10ሺ ሜትር ሊመዘገብ የሚችለው ሪከርድ  ከ14 ዓመታት በኋላ 25 ደቂቃ ከ32.27 ሰኮንዶች ከ26 ዓመታት በኋላ ደግሞ 25 ደቂቃ ከ04.36 ሰከንዶች ሲሆን 23 ደቂቃ ከ36.89 ሰከንዶች የመጨረሻው የሪከርድ ወሰን ነው፡፡
በዓለም የቤት ውስጥ  የአትሌቲክስ ውድድሮች በወንዶች 5ሺ ሜትር ኃይሌ ገብረስላሴ ለሶስት ጊዜ ሪከርዶች ቢያስመዘግብም አሁን ያለውን ሪከርድ በ2004 እኤአ በእንግሊዝ በርሚንግሃም 12 ደቂቃ ከ49.60 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ በተመሳሳይ በሴቶች የ5ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ብርሃኔ አደሬ በ2004 እኤአ፤ ጥሩነሽ ዲባባ በ2005 እና በ2007 እኤአ ካስመዘገቧቸው ሶስት ሪከርዶች በኋላ አሁን ተመዝግቦ ያለውን ሪከርድ ከ2009 እኤአ ጀምሮ ተቆጣጥራ የምትገኘው በስቶክሆልም ርቀቱን በ14 ደቂቃ ከ24.37 ሰኮንዶች የጨረሰችው መሰረት ደፋር ናት፡፡ ዘንድሮ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሮች ሁለት አዳዲስ ሪከርዶች ያስመዘገበችው ደግሞ ገንዘቤ ዲባባ ናት፡፡ ገንዘቤ በስዊድን ስቶክ ሆልም የ3ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድን 8 ደቂቃ ከ16.60 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ከማስመዝገቧም በላይ በካርሉስርህ ጀርመን በተካሄደ የ1500 ሜትር ውድድር ደግሞ ርቀቱን በ3 ደቂቃ ከ55.17 ሰከንዶች የሆነ የሪከርድ ጊዜ አስመዝግባ ማሸነፏ ይታወሳል፡፡
በጎዳና ላይ ሩጫዎች እና በልዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች በኢትዮጵያውያን የተመዘገቡ ሌሎች ክብረወሰኖችም አሉ፡፡  ኃይሌ ገብረስላሴ በዚህ ምድብ ሶስት ሪከርዶች ተመዝግበውለታል፡፡ የመጀመርያው በ20ሺ ሜትር የትራክ ውድድር በ2007 እእእ በቼክ ኦስትራቫ 56 ደቂቃ ከ25.98 ሰከንዶች በማስመዝገብ የያዘው  ሲሆን ሌላው ደግሞ በ10 ማይል የጎዳና ላይ ሩጫ  በ2005 እኤአ በቲበርግ ሆላንድ ውስጥ 44 ደቂቃ ከ23 ሰከንዶች የጨረሰበት ናቸው፡፡ በ2007 እኤአ ላይ በቼክ ኦስትራቫ በ1 ሰዓት ውስጥ በሚሸፈን ርቀት የተመዘገቡ ሁለት ሪከርዶችንም ኢትዮጵያውያን አስመዝግበዋል፡፡ ይሄውም በ1 ሰዓት ውስጥ በኃይሌ ገብረስላሴ የተሮጠው 21285 ሜትር እና በድሬ ቱኔ የተሸፈነው 18517 ሜትር ርቀት ናቸው፡፡ በተያያዘ በዓለም ትልልቅ ማራቶኖች የቦታዎቹን ሪከርድ በማስመዝገብ የኢትዮጵያ አትሌቶች ከኬንያውን ይፎካከራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ወንዶች  ከተያዙ የትልልቅ ማራቶኖች የቦታ ክብረወሰኖች መካከል ባለፈው ሳምንት ቀነኒሳ በመጀመርያው ማራቶኑ ፓሪስ ላይ  ያሸነፈበት 2 ሰዓት ከ05 ደቂቃዎች ከ 4 ሰከንዶች፤ በዱባይ ማራቶን በ2008 እኤአ ላይ አትሌት ኃይሌ ያስመዘገበው 2 ሰአት ከ04 ደቂቃ ከ53 ሰከንዶች፤ በኒውዮርክ ማራቶን በ2001 እኤአ ላይ ተስፋዬ ጅፋር በ2 ሰዓት ከ07 ደቂቃዎች ከ43 ሰኮንዶች የሆነ ጊዜ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የበርሊን፤ የቦስተንና  የሮተርዳምን የቦታ ሪከርዶች ኬንያውያን ይዘውታል፡፡
ኢትዮጵያዊ የዓለም ሻምፒዮና የኦሎምፒክ ሪከርዶች
በዓለም አትሌቲክስ  ሻምፒዮና ላይ በወንዶች ምድብ   ኬንያውያን በ800፤ በ3ሺ መሰናክል፤ በ5ሺ ሜትር እና በማራቶን ያሉ ሪከርዶችን በመቆጣጠር ከኢትዮጵያውያን ይልቃሉ፡፡ በወንዶች ምድብ  በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ  ሪከርድ ይዞ የሚገኝ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሲሆን በ2009 እኤአ በርሊን ላይ ርቀቱን በ26 ደቂቃ ከ46.31 ሰኮንዶች በመሸፈን ባስመዘገበው ጊዜ ነው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ   በሴቶች ምድብ ከተመዘገቡ ሪከርዶች የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለት ውድድሮች ሲጠቀሱ አንዲትም ኬንያዊ አትሌት የለችበትም፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በ5ሺ ሜትር ሴቶች 14 ደቂቃ ከ38.59 ሰኮንዶች የሆነ ጊዜን  ሄልሲንኪ ላይ በ2005 እኤአ  እንዲሁም በ2003 እኤአ ፓሪስ ላይ ብርሃኔ አደሬ በ10ሺ ሜትር 30 ደቂቃ ከ04.18 ሰኮንዶች በሪከርድ እንደተመዘገበላቸው ነው፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ በወንዶች  በ5ሺ ሜትር እና በ10ሺ ሜትር ሁለት ክብረወሰኖችን የያዘው  ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ሁለቱንም የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች እኤአ በ2008 በቤጂንግ በተካሄደው 29ኛው ኦሎምፒያድ ሲያስመዘገባቸው በ5 ሺ ሜትር 12 ደቂቃ ከ57.82 ሰኮንዶች እንዲሁም በ10ሺ ሜትር 27 ደቂቃ ከ04.7 ሰኮንዶች የሰፈሩ ናቸው፡፡ ኬንያውያን በ800፤ በ1500፤ በ3ሺ መሰናክልና በማራቶን የተያዙ የኦሎምፒክ ሪከርዶችን በመቆናጠጥ የተሻለ ውክልና አላቸው፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ በሴቶች ምድብ በተመዘገቡ ሪከርዶች ኢትዮጵያ በሁለት አትሌቶች ስትጠቀስ ኬንያ ግን አንድም አላስመዘገበችም፡፡ በኢትዮጵያውያን የተያዙት ሁለት የረጅም ርቀት የኦሎምፒክ ሪከርዶች በ2008 እእአ ላይ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺ ሜትር  29 ደቂቃ ከ54.66 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችውና በ2012 እኤአ ላይ በለንደን በተካሄደው 30ኛው ኦሎምፒያድ ቲኪ ገላና በማራቶን ስታሸንፍ ርቀቱን የሸፈነችበት 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ07 ሰኮንዶች ናቸው፡፡

     አብዱልአዚዝ ሳዑድ፣ የዛሬ 90 አመት ግድም ነው፣ ተቀናቃኝ የጎሳ መሪዎችንና የጦር አበጋዞችን በማንበርከክ ዙፋን ላይ የወጡት። የሳዑዲ ቤተሰብ፣ ገናና የንጉሥ ቤተሰብ በመሆን የታሪክ ጉዞውን የጀመረው ያኔ ነው። አገሪቱ በራሳቸው ቤተሰብ ስም “ሳዑዲ አረቢያ” ተብላ እንድትጠራ የወሰኑት አብዱልአዚዝ ሳዑድ፣ ለ20 አመታት ገዝተዋል። ዘኢኮኖሚስት መፅሄት በዚህ ሳምንት እትሙ፣ እንደገለፀው አብደልአዚዝ ብዙ ወራሾችን ትተው ነው የሞቱት - 36 ልጆችን።
ወራሽ ሲበዛ ምን እንደሚፈጠር ይታወቃል። ቤተመንግስትና አገር ይረበሻል። በእርግጥ አብዱልአዚዝ ከመሞታቸው በፊት የበኩር ልጃቸውን በአልጋ ወራሽነት አዘጋጅተውታል። በቀብራቸው ማግስት፣ የስልጣን ሽኩቻ መፈጠሩ ግን አልቀረም። በተለይ በሁለቱ ታላላቅ ልጆች (በሳዑድ እና በፋይሳል) መካከል የነበረው ትንቅንቅ ቀላል አይደለም። ታላቅዬው ወንድም “ሳዑድ አብደልአዚዝ ሳዑድ” ቀደም ሲል አልጋ ወራሽ ተብለው መሰየማቸው ጠቀማቸው። በስንት መከራ የመጀመሪያውን ዙር ትግል አሸንፈው ዙፋኑን ለመቆጣጠር በቅተዋል። ታዲያ፤ ታናሽ ወንድማቸው “ፋይሳል አብዱልአዚዝ ሳዑድ”፣ እጅ ሰጥተው አልተቀመጡም። ተቀናቃኝነታቸው ለአንድም ቀን አልረገበም። እንዲያውም ባሰበት። የሁለቱ ፀብ ለአምስት አመታት ሲባባስ ቆይቶም ነው፤ በ1950 ዓ.ም የፈነዳው። በየራሳቸው ጎራ ተከታይና አጃቢ አደራጅተው፤ የሹም ሽረታቸውን ተፋጠጡ። ሁለተኛው ዙር ግብግብ ልንለው እንችላለን።
ልዑል ፋይሳል፣ ሙሉ ለሙሉ ታላቅ ወንድማቸውን ከስልጣን ፈንቅለው ለመጣል ባይችሉም፤ በዚህ የሁለተኛው ዙር ትንቅንቅ በከፊል ቀንቷቸዋል። “ንጉሡ አገሪቱን በወጉ እያስተዳደሩ አይደለም፤ ገንዘብ አያያዝም አይችሉበትም” በማለት ከፍተኛ ዘመቻ ያካሄዱት ልዑል ፋይሳል፤ ዙፋኑን ቢወርሱ ደስታቸው ነበር። ያ አልሆነም። ነገር ግን፤ በከፊል የንጉሡን ስልጣን ሸርሽረው ለመውሰድ በቅተዋል። በሽኩቻው ልዑል ፋይሳል የበላይነት እንዳገኙ በግልፅ የታየው፤ የአገሪቱ መሳፍንትና የሃይማኖት መሪዎች ተሰብስበው በወቅቱ ያወጧቸው ሁለት አዋጆች በይፋ ከተነገሩ በኋላ ነው። አንደኛ፤ ቀደም ሲል ፅህፈት ቤት ሲባሉ የነበሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተብለው እንዲሰየሙ ተወሰነ። ከዚህም ጋር ተያይዞ፤ ልዑል ፋይሳል የአገሪቱ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል ተባለ። ሁለተኛ፤ ንጉሡ፣ ከጥግ እስከ ጥግ ጠቅልለው የያዙትን ስልጣን፣ ለሌሎች ማጋራትና ማካፈል እንዳለባቸው በመሳፍንቱና በሃይማኖት መሪዎች ተሰብስበው ወስነዋል። የመንግስት ስራዎችን በበላይነትና በብቸኝነት የመምራት ስልጣን የነበራቸው ንጉሥ ሳዑድ፣ ስልጣናቸውን ለማን እንዲያጋሩ ይሆን የተወሰነባቸው? ምን ይጠየቃል! ለወንድማቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ፋይሳል ነዋ!
የንጉሡ ገደብ የለሽ “የፈላጭ ቆራጭ” ስልጣን፣ በአዲስ የስልጣን ክፍፍል ተቀየረ ተብሎ ታወጀ። አዲስ ዘመን ተጀመረ ተብሎ ተበሰረ። በእርግጥ፤ ንጉሡ ማንኛውንም ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ የመሻር ስልጣን ይኖራቸዋል። ነገር ግን “ውሳኔ የመሻር” ስልጣንና፣ “ውሳኔ የማስተላለፍ” ስልጣን ይለያያሉ። ውሳኔዎችን የማስተላለፍና የመንግስት ስራዎችን የመምራት ስልጣን፣ ለጠ.ሚ. ፋይሳል ተሰጥቷል። የወንድማማቾቹ ሁለተኛ ዙር ትንቅንቅ፣ በዚሁ አበቃ። ሽኩቻቸው ግን አልቆመም። ወዲያውኑ ወደ ሶስተኛ ዙር ትግል ተሸጋግረዋል። ስልጣን የተቀነሰባቸው ንጉሥ፤ እንደገና ሁሉንም ስልጣን ጠቅልለው ለመውሰድ ሁለት አመት አልፈጀባቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይሳል ከስልጣን ለቀቁ።
የቤተሰብና የዘመድ ፀብ ቶሎ አይበርድም። ፋይሳል በቃ ተሸነፍኩ ብለው በዚያው አልቀሩም። ለአራት አመታት ቲፎዞ ሲያሰባስቡና ዝግጅት ሲያካሂዱ የቆዩት ፋይሳል፤ ከቀድሞው የላቀ ጉልበት በመያዝ ከሃያሉ ንጉሥ ጋር አራተኛውን የስልጣን ትንቅንቅ ገጠሙ። ይሄኛው ዙር፣ የሹም ሽረት ብቻ ሳይሆን የሞት ሽረት ግብግብ ነው ቢባል ይሻላል። ፋይሳል አልተቻሉም። የቀድሞ ስልጣናቸውን ከንጉሡ በመንጠቅ ብቻም አልተመለሱም። አልጋ ወራሽ ሆነው እንዲሰየሙ ቢደረግም፤ አላረካቸውም። በጥቂት ወራት ውስጥ፣ በ1957 ዓ.ም አልጋ ወራሽ ፋይሳል፣ በሽኩቻው ተሳክቶላቸው ወንድማቸውን ከስልጣን በማባረር ዙፋኑን ተቆጣጠሩ። በንጉሥና በጠቅላይ ሚኒስትር መካከል የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ለአመታት ሲከራከሩ የነበሩት ፋይሳል፣ ሃሳባቸውን ለመቀየር ጊዜ አልፈጀባቸው። ዘውድ እንደደፉ፣ ወዲያውኑ ሁሉንም ስልጣን ለራሳቸው ጠቅልለው ወሰዱት። ስልጣን የሚቀናቀን ጠቅላይ ሚኒስትር የሚባል ነገር እንዲኖር ስላልፈለጉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ለራሴ ደርቤ ይዤዋለሁ ብለው ገቢ አደረጉት።
ከዚያ በኋላ፣ ንጉሥ ፋይሳል እንደተለመደው ሌሎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ለወንድሞቻቸው አከፋፍለዋል። ከሚኒስትርነት ቦታ በተጨማሪ፣ የጦር ሃይል፣ የክብር ዘብ እና የስለላ ድርጅቶችን በሃላፊነት የሚመሩትም የንጉሡ ወንድሞች ናቸው። አገሬውን በሙሉ በቤተሰባችን ቁጥጥር ውስጥ ገባ ብለው በደስታ የሚፈነጥዙ ከመሰለን ተሳስተናል። በተቃራኒው፤ የሚኒስትርነትና የሃላፊነት ቦታዎችን በተቆጣጠሩ ወንድማማቾች መሃል የስልጣን ሽኩቻው ይበልጥ ይጧጧፋል። በእናት የሚገናኙ ወንድማማቾችና በእናት የሚለያዩ ወንድማማቾች እንዴት እንደሚተያዩ አስቡት።
እንዲያም ሆኖ፣ ፋይሳል ብዙም አልተቸገሩም። ያኔ የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ በነበረት ጊዜ፣ ንጉስ ፋይሳል ተመቻቸው። አገሬውን በድጎማ አንበሸብሸዋለሁ ከማለታቸውም በተጨማሪ፣ ከወንድማቸው ስልጣን ለመንጠቅ ባካሄዱት ረዥም የትግል ወቅት ከጎናቸው ሆነው ላገዟቸው የሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እየሰጡ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ወንበራቸውን አደላድለዋል። ንጉሥ ፋይሰል የተደላደለ ዙፋን ላይ አስር አመት ከደፈኑ በኋላ ነው፤ ቤተመንግስታቸው ውስጥ እንደወትሮው ዘመድ አዝማድ የንጉሥ ቤተሰቦችን እያነጋገሩ ሳለ የተገደሉት። የደበቀውን ሽጉጥ እዚያው ከፊት ለፊታቸው አውጥቶ የገደላቸው፣ የወንድማቸው ልጅ ነው - ለዚያውም በሳቸው ስም ፋይሳል ተብሎ የተሰየመ ወጣት ልዑል። በበርካታ ጥይቶች የቆሰሉት አዛውንቱ ፋይሳል፣ ወዲያውኑ  ወደ ሆስፒታል ተወስደው በሐኪሞች ሲከበቡ፤ ወጣቱ ፋይሳል ደግሞ ወደ እስር ቤት ተወስዶ መርማሪዎች በጥያቄ እያፋጠጡት ነበር።  አዛውንቱ ፋይሳል፤ የመዳን እድል አልነበራቸውም። ብዙም ሳይቆዩ ነው የሞቱት። ወጣቱ ፋይሳልም፣ ለረዥም ጊዜ በሕይወት አልቆየም። በእርግጥ ድርጊቱን የፈፀመው፣ ብዙዎች እንደጠረጠሩት መንግስት ለመገልበጥና ዙፋን ለመውረስ ታስቦ በተቀነባበረ ሴራ አማካኝነት አይደለም። ለመርማሪዎች በሰጠው ቃል ፤ “ንጉሡ የሃይማኖት አክራሪነትን እያበረታቱ አገሪቱን ወደ መጥፎ አቅጣጫ እየወሰዷት ነው” በሚል እምነት ግድያውን እንደፈፀመ ገልጿል።
የሆነ ሆኖ፤ ሕይወት ትቀጠላለች። በፋይሳል ምትክ ታናሽ ወንድም ልዑል ካሊድ ዘውድ ወርሰው ነገሡ። ካሊድ፣ እንደሌሎቹ ወንድማማቾች፣ የስልጣን ሽኩቻን የማዘውተር ዝንባሌና ፍላጎት አልነበራቸውም። እንዲያውም፤ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በክብር እንግድነት ከመገኘት በስተቀር፤ ከቤተመንግስትና ከስልጣን ያን ያህልም ቅርርብ ዝምድና አልፈጠሩም። ምናልባት ከቤተመንግስትና ከስልጣን ሹክቻ ጋር የተራራቁት፤ ብዙውን ጊዜ ጤንነት ስለማይሰማቸው ሊሆን ይችላል። ከአንድም ሁለት ሶስቴ በጠና ታመዋል። በልብ ህመም ተይዘው፣ ከሞት የተረፉት በቀዶ ህክምና ነው። ይሄ ሁሉ፣ ስልጣን ከመውረስ አላገዳቸውም። በቃ! በሕይወት ካሉት ወንድማማቾች ሁሉ በእድሜ ታላቅ ስለሆኑ ተራ ደርሷቸው ነገሡ። ለካ፤ ንጉሥ መሆንና ሥልጣን መያዝ፣ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ንጉሥ ካሊድ፣ አብዛኛውን ስልጣን ለታናሽ ወንድማቸው ለልዑል ፉዓድ በውክልና የሰጧቸው በወራት ውስጥ ነው። ህመም የተደራረበባቸው ንጉሥ ካሊድ፣ ብዙም ጤና ሳያገኙ ሰኔ 1974 ዓ.ም እንዳረፉ፤ ወዲያው ዙፋኑ ላይ የተተኩትም ልዑል ፉዓድ ናቸው።
ፉዓድ ቀድሞውንም በጠቅላይ ሚኒስትርነት አብዛኛውን ስልጣን ስለተቆጣጠሩ፤ የነገሡ ጊዜ ብዙም የተለወጠ ነገር አልነበረም። አራቱ ወንድማማቾች በየተራ እንደየእድሜያቸው ቅደም ተከተል ስልጣን ላይ የወጡት፤ አባታቸው አብዱልአዚዝ አስቀድመው በተናገሩት ትዕዛዝ መሰረት ነው። ታላቅ ወንድም እያለ፣ ታናሽ ወንድም ንጉሥ እንዳይሆን ተናዝዘው ነው የሞቱት። ተራ ደርሷቸው ስልጣን የያዙት ፉዓድ፣ የክብር ዘብ አዛዥ የነበሩ ታናሽ ወንድማቸው ልዑል አብዱላህ አልጋ ወራሽና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ መሰየም ነበረባቸው - የአባታቸውን ኑዛዜ ላለመሻር እንጂ ከልዑል አብዱላህ ጋር ብዙ አይዋደዱም ነበር።
ንጉሥ ፉዓድ በ60ኛ እድሜያቸው ዋዜማ ዙፋን ላይ ለመውጣት መብቃታቸው፤ እንደ ትልቅ እድል ይቆጠርላቸዋል። ለምን ቢባል፤ በእድሜ ከፉዓድ የሚበልጡ ወንድማማቾች ሁሉ በየተራ ቢነግሱ ኖሮ፤ ፉዓድ እንዲያ በፍጥነት ተራ ባልደረሰባቸው ነበር። ነገር ግን እድል ያላለላቸው ልጆች፣ በመሃል በተለያየ ምክንያት ይሞታሉ። ለዚህም ነው ፉዓድ 11ኛ ልጅ ሆነው ሳለ፤ ስልጣን በመያዝ ግን አራተኛ ናቸው። በዚያ ላይ ከሃያ አመታት በላይ በስልጣን ላይ ለመቆየት ችለዋል - እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ። ያው ፉዓድ ሲሞቱ፤ አምስተኛው ተረኛ ልዑል አብዱላህ ስልጣን ተረክበው፤ ይሄው እስከ አሁን  ዙፋን ላይ ናቸው።
“ወንድማማቾች ዙፋኑን ይፈራረቁበታል!” ብሎ መናገር ቢቻልም፤ በዚያው መጠን ንግሥና አፋፍ ላይ ደርሰው በአካል ለማጣጣም ሳይታደሉ ያመለጣቸው “እድለቢስ” ልዑላን ጥቂት አይደሉም። ለምሳሌ፤ የአብዱላህ ታናሽ ወንድም፣ “ልዑል ሱልጣን”ን መጥቀስ ይቻላል። በእርግጥ፣ ልዑል ሱልጣን፣ ያን ያህልም ስልጣን አነሳቸው የሚባልላቸው አይደሉም። ለአርባ አመታት ያህል በመከላከያ ሚኒስትርነት የቆዩ ናቸው። ከዚያም በተጨማሪ ንጉሥ አብዱላህን ለመተካት፣ አልጋ ወራሽ ተብለው ተሰይመዋል። ግን አልጋ ሳይወርሱ ነው ከዛሬ ከሶስት አመት በፊት የሞቱት። በአገሪቱ ውስጥ ቁልፍ የስልጣን ቦታ ነው በሚባለው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርነት ላይ ከሰላሳ አመታት በላይ የቆዩት ልዑል ናይፍ ደግሞ፣ አልጋ ወራሽ ተብለው በተሰየሙ በአመታቸው ሕይወታቸው አልፏል። በሳቸው ምትክ አልጋ ወራሽ እንዲሆኑ የተደረጉት ልዑል ሳልማን ናቸው።
ነገር ግን የልዑል ሳልማን እጣ ፋንታም ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም። ንጉሥ ለመሆን ተስፋ ያላቸው አይመስልም። እድሜያቸው ገፍቷል። 78 ዓመታቸውን ደፍነዋል። በዚያ ላይ፣ ከእድሜ ጋር አብሮ የሚከሰት የመርሳት ህመም ሳያጠቃቸው አይቀርም ተብሎ ይገመታል። ለዚህም ይመስላል፤ ንጉሥ አብዱላህ ከሳምንት በፊት፣ በሳዑዲ አረቢያ እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ አዲስ አዋጅ ያስነገሩት።
የአዋጁ አዲስነት ምኑ ላይ ነው? አንደኛ፤ ተተኪ አልጋ ወራሽ ለመሰየም አዋጅ ማስነገር የተለመደ ነገር ነው። አዲሱ አዋጅ ከዚህ ይለያል። የተተኪ ተተኪ አልጋ ወራሽ ለመሰየም የወጣ አዋጅ ነው። በሳዑዲ አረቢያ የዘጠና አመት ታሪክ ውስጥ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተተኪ ተተኪ አልጋ ወራሽ በአዋጅ የተሰየመው። ሁለተኛ፤ እስከዛሬ በነበረው አሰራር፣ ከወንድማማቾቹ መሃል በእድሜ ታላቅ የሆነው ነበር በአልጋ ወራሽነት እየተሰየመ የሚነግሰው። የአሁኑ ግን፤ የእድሜ ቅደም ተከተልን ያልተከተለ ነው። ያለ ምክንያት አይደለም።
ከ36ቱ ወንድማማቾች መካከል 15ቱ አሁንም በሕይወት አሉ። ነገር ግን ብዙዎቹ እንደ ልዑል ሳልማን እድሜያቸው ስለገፋ፣ ንጉሥ የመሆን እድላቸው አነስተኛ ነው። በሕይወት ካሉት ወንድማማቾች መካከል ከእንግዲህ ንጉስ የመሆን እድል የሚኖራቸው የሁሉም ታናሽ የሆኑት የ60 ዓመቱ ልዑል ሙቅሪን ናቸው። ለበርካታ አመታት የአገሪቱን የስለላ ድርጅት በሃላፊነት የመሩት ልዑል ሙቅሪን፣ የእድሜ ቅደም ተከተል ሳይጠብቁ በአልጋ ወራሽነት እንዲሰየሙ ተደርጓል። መቼ እንደሚነግሱ  ባይታወቅም፤ ከግማሽ ምዕተዓመት በላይ ያስቆጠረው የወንድማማቾች የስልጣን ሽኩቻና የዘውድ ቅብብል ወደ ማብቂያው የተቃረበ ይመስላል። እውነታው ግን ከዚህ ይለያል።
ሽኩቻውና ቅብብሉ ወደ ማብቂያው የተቃረበ ይመስላል እንጂ፤ “ገና ምኑ ተጀመረ?” ቢባል ይሻላል። ንጉሥ ለመሆን፣ ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ወፍራም ስልጣን ለማግኘት የሚጠባበቁ “ልዑላን”፣ ዛሬ እንደድሮው 36 ብቻ አይደሉም። የአብዱልአዚዝ ልጆች፣ የስልጣን ዘመናቸው ሲያበቃ፤ በቦታው ከአንድ ሺ በላይ የልጅ ልጆች ተተክተዋል። የስልጣን ሽኩቻው፤ በሺህ ልዑላን መካከል ሆኗል።
 የንግሥና ቅብብሎሹ ደግሞ፣ ለሺህ ልዑላን ሊዳረስ አይችልም። ተራው የደረሳቸው ልዑላን፤ በአብዛኛው ከአስር አመት በላይ ነው በንግሥና የሚቆዩት። የአምስት ወንድማማቾች ዘመነ መንግስት ሲደማመር፤ ከ60 ዓመት በላይ ሆኗል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ ቀሪዎቹ ወንድማማቾች ብቻ ሳይሆኑ፣ ልጆቻቸውም በእድሜ ገፍተው እያረጁ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። የልጅ ልጆች በብዛት መጥተዋል። በጥቂት አመታት ውስጥ፣ የሳዑዲ ልዑላን ቁጥር ወደ ስምንት ሺ ገደማ እንደሚደርስ የጠቀሰው ዘኢኮኖሚስት፤ አንዳንዶቹ ልዑላን ተራ የመጠበቅ ትዕግስታቸው እየተሟጠጠ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃል። በሌላ አነጋገር፤ በማንኛውም ቀን ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም፡፡
በጥንታዊ የጐሳና የዘር ትስስር ላይ ተሞርኩዞ የተጀመረው የአብዱልአዚዝ ስርወመንግስት፤ ገና በጥዋቱ በቤተሰብ አባላት ወይም በወንድማማቾች ሽኩቻ መወሳሰቡ ሳያንስ፤ ዛሬ  መፍትሔ ወደሌለው የእልፍ ልዑላን የስልጣን ሽሚያ እያመራ ነው፡፡
አንድ በሉ፡፡ የሳዑዲ ንጉሳዊ ቤተሰብ ሌላ ምርኩዝ ሃይማኖት ነው፡፡ ለምን ቢባል፤ በአክራሪነት ዝንባሌ ከሚጠቀሰው የዋሃቢያ አስተምህሮ ጐን በአለኝታነት በመሰለፍ ስልጣን ላይ ለመውጣትና ለመደላደል ችሏል፡፡
ነገር ግን፤ የስልጣን መደላደል ሲሆንላቸው የነበረው የሃይማኖት ነገር፤ ቀስ በቀስ የአደጋ ምንጭ እየሆነባቸው ነው፡፡ ሳዑዲ እነ ኦሳማ ቢን ላደኖችን የምትፈለፍል አገር ሆናለችና፡፡ ሁለት በሉ፡፡
የሳዑዲ ንጉሳዊ መንግስት ሦስተኛው መተማመኛ፤ በመንግስት ቁጥጥር ውስጥ የገባው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ነገር ግን በነዳጅ ሃብት ቀዳሚ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ዛሬ ዛሬ ለዜጐቿ ተስማሚ አልሆነችም፡፡ መንግስት ገንዘብ እያፈሰሰ ድጐማ ማከፋፈል አላቃተውም፡፡ ምን ዋጋ አለው? ተመጽዋችነት፤ በራስ ጥረት ራስን ችሎ እንደመኖር አያረካም፡፡ ለዚህም ነው የሳዑዱ ስራ አጥ ወጣቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቅሬታቸው እየተባባሰ ወደ ቀውስ እያመራ የመጣው፡፡ ሦስት አትሉም፡፡
በአጠቃላይ፤ የሳዑዲ መንግስት እንደመተማመኛ የያዛቸው ሦስት ነገሮች (የጐሳ፣ የሃይማኖትና የድጐማ አቅጣጫዎች) ለአደጋ የሚያጋልጡ የቀውስ ምንጮች መሆናቸው በገሃድ እየታየ ነው፡፡ እነዚህ ሦስት የቀውስ አቅጣጫዎች ሳዑዲን ብቻ የሚያጠቁ ችግር አይደሉም፡፡ አለምን ከዳር ዳር ከሚያናጉ ሦስት የዘመናችን የቀውስ ምንጮች መካከል ሁለቱ የጐሳና የብሔር ጉዳይ እና የሃይማኖት አክራሪነትና የሽብር አቅጣጫዎች መሆናቸውን ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ - የብዙ አገሮችን መረጃ በመጠቃቀስ። ከድጐማ ጋር ወደተያያዘው ሦስተኛ የቀውስ ምንጭ ለመሸጋገር ነው የሳዑዲዎቹን ታሪክ በአጭሩ የተረኩላችሁ፡፡ 

Published in ከአለም ዙሪያ
Monday, 14 April 2014 10:23

ድራግ - የሰሞኑ ወሬ

ከወንዱ ዘር ይልቅ የሴቷ ዘር ካናቢስ የበለጠ ተፈላጊ ነው፡፡ የካናቢስ ተክል እንደ ፓፓያ ተክል የወንድና ሴት ዝርያ አለው፡፡ የወንድ ፖፖያ ተክል የሚፈለገውን ፍሬ አይሰጥም ግን እሱ ከሌለ ሴቷ ፍሬ አትሰጥም፡፡ በካናቢስ በኩል ደግሞ ሴቷ በገበያው ላይ የበለጠ ተፈላጊ ነች (ወንድና ሴቱ በምን ይሆን የሚለዩት?)፡፡ ለምን የበለጠ ተፈላጊ ሆነች? ከተባለ ያችን ማነቃቂዋን ንጥረ ነገር (Psychoactive principle – tetrahy drocannabinol – THC)   የበለጠ የምትሸከመው እሷው ስለሆነች ነው፡፡ ቅጠሉም፣ አበባውም፣ ፀጉሯም በተለያየ መጠን ይህን ሥሙ ረዥም የሆነ ንጥረ ነገር ቲኤችሲ THC ትይዛለች፡፡ ዋጋውም ቅጠሉ ሌላ፣ አበባው ሌላ ሁሉም የየራሣቸው ተመን አላቸው፡፡ የት ነው የሚገኘው ብሎ ጠያቂ አለ?
እንዲያው ዋናው ንጥረ ነገር በሴቷ ካናቢስ በከፍተኛ መጠን ይገኛል ይባል እንጂ በጥቅሉ ካናቢስ ከ400 በላይ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ጉድ ነገር ነው (የአማርኛው ጉድ) ከእነዚህ ውስጥ 60 ያህሉ ንጥረ ነገሮች ዋና ዋና ሡሥ አምጭዎች፣ አነቃቂዎች፣ አደንዛዦች፣ አእምሮና አካል ገዥዎች፣ በሽታና ሞት ጠሪዎች፣ ጓደኛና ቤተሰብ አባራሪዎች (የሆናችሁትን ሁሉ ማድረግ የሚችሉ) ናቸው፡፡ ዋናው ግን ቀደም ብለን ያነሳነው ንጥረ ነገር ቲኤችሲ ሲሆን ይህ ንጥረ ነገር በማሪዋና ውስጥ በትንሹ ከአንድ በመቶ ጀምሮ እስከ 15 በመቶ ድረስ ይገኛል፡፡
ማሪዋናን መጥቀሴ በአብዛኛው ገበያ ላይ ከሚገኙት ምርቶች ውስጥ ማሪዋናና ሃሽሽ (በተለያየ ቦታ የተለያየ መጠሪያ አላቸው) እነዚህ በቀዳሚነት ስለሚነሱ ነው፡፡ የተፈጥሮአቸውን ጉዳይ ለተመራማሪዎቹ ትተን እነዚህን ዕፆች በሚወስዱ ሰዎች ላይ የሚከተለውን አእምሯዊም በሉት ሥነ ልቦናዊ፣ የባህሪም ይሁን የስነልቦና፣ አካላዊም በሉት ማህበራዊ ጫናዎቹ ምን እንደሚመስሉ ለመመልከት እንሞክር፡፡  
ዘመናዊ የህክምና መሳረያዎች የአንጎልን ሥርዓትና ዕድገት ሁኔታ ለማጥናትና ለመረዳት ትልቅ እገዛ አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት እድሜአቸው እስከ 24 የሚደርሱ አፍላ ወጣቶች አንጎላቸው ሙሉ በሙሉ እድገቱን አይጨርስም፡፡ በተለያየ መነሻ በአፍላ እድሜ የማሪዋና፣ የሲጋራ ወይም የአልኮል መጠጥ የሞከረ አንድ ግለሰብ በወጣትነቱና በጎልማሳ የእድሜው ደረጃ ላይ በሱስ የመጠመድ እድሉ ሰፊ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ የአፍላነት እድሜ ታዳጊ ውጣቶች ማሪዋናን እንደ ቀላል ጉዳይ አንሰተው ሊሞክሩ ይችላሉ፡፡ ምክንያታቸውም ጓደኛን ለመምሰል፣ ለመዝናናት፣ ከድብርት ለመውጣት፣ ከአዋቂዎች ጎራ የተቀላቀሉ ዓይነት ስሜት ለመፍጠር፣ መሳሰሉት ቀላል መነሻዎች ሊሆን ይችላል፡፡ ክፋቱ ግን ማሪዋናን ለመጀመር የሚቀለውን ያህል ለመተው የሚያስችል ሠፊ መንገድ የለም፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው እነዚያ ንጥረ ነገሮች እንደሚወሰደው መጠን በደቂቃዎች፣ በሰዓታት ወዘተ በደም ውስጥ እየሰረጉ ይገባሉ፡፡ ከግለሰቡ ጋር ቁርኝት ይፈጥራሉ፡፡ በነገራችን ላይ ማሪዋናን ለሙከራ በሚል ከሚወስዱ ስድስት ሠዎች ውስጥ አንዱ በዛው ሠምጦ ይቀራል፡፡ በእርግጥ አብዛኞቹ ወጣቶች ወደዚህ ሱስ የሚገቡት በጓደኛ ተፅዕኖ ነው፡፡ በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ለሌላ ሃይል አይኑራቸው እንጂ ጓደኛን ለመጎተት ብርቱ ናቸው፡፡ አፍላ ወጣት ነህ ሁሉን መሞከር አለብህ፣ ሞክረህ በሚሉና በተለያዩ ማሳመኛቸው ግብዣውን ሁሉ በማቅረብ ወይም ላያቸው ላይ በማጨስ ሊስቡ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው፡፡
ማሪዋና ጀማሪዎች ላይ መውሰድ ከጀመሩባቸው ቀናት አንስቶ አንዳንድ ያልተለመዱ ለውጦች ይስተዋላሉ፡፡ ለምሳሌ የአይን መቅላት፣ የጿጉርና የልብሳቸው ጠረን መለወጥ፣ የማስታወስ ሁኔታ መቀነስ፣ ባልተለመደ ሁኔታ ቀላል ሥህተቶችን መፈፀም፣ ዘወትር ከሚገኙባቸው ቦታዎች መራቅ፣ ጓደኛ መለወጥ፣ ከዘመድ አዝማድና ቤተሰብ መራቅ ይጀመራል፡፡ ይቀጥላል የድብርት ሥሜት ይንፀባረቃል፣ በእግር ሲጓዙ መድከም፣ እንቅልፍ ማጣት ወይም አብዝቶ መተኛት፣ ለነገሮች ምላሽ ለመስጠት መዘግየት፣ ከምክንያታዊነት መውጣት ወይም ምክንያታዊ መሆን አለመቻል፣ የንግግር ሁኔታ መፋለስ፣ የአፍ ጠረን መለወጥ፣ የጥርስ መበላሸት፣ ዘወትር የሚያከናውኗቸውን ጉዳዮች ከማድረግ መሥነፍ ወዘተ፡፡
እንዲህ ይላል አንድ ሰው ቀልቡ መለስ ሲልለትና የሆነውን ሁሉ መለስ ብሎ ለማሰብ ሲሞክር “ይነጋል ይመሻል እኔ ግን የጊዜ ልዩነት አይገባኝም... ብቻ የምፈልገው ነገር ወዳለበት እየተንሰፈሰፍኩ እከንፋለሁ፣ አገኛዋለሁ እየተንሰፈሰፍኩ እወስደዋለሁ፣ እወጣለሁ፣ እሞቃለሁ እንደገና እወርዳለሁ፣ እቀዘቅዛለሁ፡፡ ራሴን መጥላት ጀመርኩ፣ ከጓደኞቼ ከቤተሰቤ ተለያየሁ፣ እፈራለሁ፣ ሁሉንም ነገር ሁሉንም ሰው እፈራሁ ብቻዬን ቀረሁ...”
አደንዛዥ ዕፅ በአንጎል ውስጥ በተለይ ለማስታወስ በሚረዳን ክፍል ላይ ተፅዕኖ ያሣድራል፡፡ ራሳችንን፣ ዓለምን፣ አካባቢንና ቤተሰብን ያስረሳል ወይም ለእነዚህ ጉዳዮች ቦታ አይሰጡም፣ ሃላፊነት አይወስዱም፣ መደበኛ ሥራቸውን ማከናወን ወደማችሉበት ደረጃም ይደርሳሉ፡፡ ተማሪዎች ከሆኑ ደግሞ የማሪዋና ክፋቱ ለተማሪ የሚያስፈልገውን ዋና ዋና ጉዳዮች ከጉያቸው ይነጥቃል፡፡ ትምህርት ትልቁ የሚሰጠን ወይም የሚያሰለጥነን ነገር በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ለምን የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ነው፡፡ ምክንያታዊ እንድንሆን ምክንያት (reason) እንድንጠይቅ ምክንያት እንድንፈልግ ነው ፡፡ ሆኖም አደንዛዥ ዕፅ ይህን የሚያከናውነውን የአንጎል ሥርዓት ያውከዋል፣ ያዳክመዋል ግለሰቡ ማብሰልሰል ይሳነዋል፡፡ ማሪዋና ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎች በሂሳብ ትምህርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከሙ ይሄዳሉ፣ ገለፃ በሚያስፈልጋቸው የትምህርት አይነቶች ራስን ወይም የተረዱትን፣ ያነበቡትን ወይም ያጠኑትን ጉዳይ መግለፅ ያቅታቸዋል ይዘበራርቃሉ፡፡ የተማሩትን ወይም ያጠኑትን መግለፅ አለመቻል ብቻ ሳይሆን ማስታወስ ሁሉ አይችሉም፡፡ የማስታወሰና የትኩረት ጉዳይ ከቀነሰ፣ ለምን ወይም አመክንዮ (reasoning) ከጠፋ፣ ማብላላትና የተወሳሰቡ ቀመሮችን መፍታት ካልተቻለ የመማር ጉዳይ አከተመለት ማለት ነው፡፡ ትምህርት ይቆማል ሥራም ከሆነ እነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ከሌሉ ጠረጴዛህን እንኳን ለማፅዳት እድል ሳታገኝ እንደወጣህ ትቀራለህ፡፡
አእምሮ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይቀጥላል ማሪዋና የሚወስዱ ሰዎች የጊዜ ቀመር ግንዛቤ አይኖራቸውም፣ የማገናዘብና የሁኔታዎችን ሚዛን መጠበቅ ያቅታቸዋል ለምሳሌ መኪና በሚያሽከረክሩበት ጊዜ የትራፊኩን እንቅስቃሴ መመዘንና (balance) መቆጣጠር አይችሉም፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ሲፈፅሙ (ችለው ካደረጉት) የሚራመዱት ሳያገናዝቡ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካን ሀገር (ለመጥፎውም ለመልካሙም ምሳሌአችን በሆነችው) በድንገተኛ የህክምና ክፍል ውስጥ በየእለቱ ከሚገኙ ታካሚዎች አብዛኛቹ በአልኮልና አደንዛዥ ዕፅ ምክንያት የደነዘዙ ወይም በዚህ ምክንያት አደጋ የደረሰባቸው ግለሰቦች ሲሆኑ በወንጀል ተጠርጥረው ከሚታሰሩ ወንዶች 40 በመቶ ያህሉ የማሪዋና ሱሰኞች ናቸው፡፡ ማሪዋናን ለመጀመር የሚቀለውን ያህል ለመተው መንገዱ ሰፊ ሥላልሆነ እነዚህ ሰዎች ታስረውም ቢሆን አለት ተደርምሶም ይሁን ማሪዋና ወዳሉበት እሥር ቤት እንዲደርስ ያደርጋሉ፡፡ ይህን ወሬ እንሰብስበውና የበዓል ሰው ይበለን፡፡
እንደዋዛ በትንሹ ይጀመራል ያነቃቃል፣ የመሰልጠን የማወቅ መስመር የገባን ይመስለናል፣ መጠኑ ከፍ ይላል (ሱስ ነውና ማለቱ አይቀርም) መቃዥትም መንቀዥቀዥም ይቀጥላል፣   መጠኑ ይበዛል አእምሮም አካልም ይፈዛል፣ ይደነዝዛል ወደ መመረዝና መመረዝ (አንዱ ላልቶ አንዱ ጠብቆ ይነበብ) ድረስ ይዘለቃል፡፡ ያሉበትን መርሳት፣ የሆኑትን አለማወቅ፣ አካልንና አእምሮን አለማዘዝ፣ ድብርት፣ የእንቅልፍ ችግር፣ የወሲብ ጓደኛን ማብዛት፣ ጥንቃቄ አለማድረግ የመሳሰሉት በአብዛኞቹ ላይ የሚታዩ ናቸው፡፡ የማሪዋና ክፋቱ ወይም ሃይሉ ደግሞ ቀደም ሲል እንዳወጋነው መርዙን በሰውነት ውስጥ ተክሎ መርጨቱና ብዙ መቆየቱ ነው፡፡ ለምሳሌ በአልኮል መጠጥ ውስጥ አንድ ንጥረ ነገር ይኖራል (ethanol) በማሪዋና ውስጥ ግን 400 የሚደርሱ ንጥር ነገሮች ይኖራሉ፡፡ በአልኮል ውስጥ ያለው ንጥረ ነገር በሰውነት ውስጥ ለሰዓታት የመቆየት አቅም ሲኖረው፤ በማሪዋና ውስጥ ያለው ግን ለሳምንታት ከዚያም በላይ ለወራት ይዘልቃል፡፡ እንደተወሰደው መጠን ሁለቱን ወይም ሲጋራን ጨምሮ ሦስቱን ቀይጠው ወይም ቀላቅለው በሚወስዱ ሠዎች ላይ ደግሞ የአእምሮ ድንዛዜ ከፋ አለ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ብዙ የማሪዋና ሱሰኞች ሲጋራና አልኮል ተጠቀሚዎች ናቸው፡፡
ማሪዋና ተጠቃሚዎች በቀላሉ ለቀላል በሽታዎች ሁሉ ይጋለጣሉ፣ በሽታን የመቋቋሚያ አቅም ያንሳቸዋል፣ በወንዶች ላይ በዘር ፈሣሽ ውስጥ የሚገኙ ህዋሳትን (Cells) ያንኮላሻል ለዚህም ትንሿ መጠን በቂ ልትሆን ትችላለች፡፡ በዚህ ወቅትም ይህ የዘር ፈሣሽ ዘር የመተካት አቅም አይኖረውም፡፡ በሴቶች ላይ የወር አበባ ዑደትን ያውካል፡፡ ማሪዋና ተጠቃሚ ከሆኑ ሰዎች የሚወለዱ ህፃናት ከመደበኛው ጊዜ ቀድመው ሊወለዱ፣ ክብደታቸው በጣም አነስተኛና የሚወለዱት ልጆች ለአካላዊ ችግር የተጋለጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌላ ሌላውን ቁጥር ትተን ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በአለማችን ማሪዋናን የሚያመርቱ ሠዎች ቁጥር በአስር እጥፍ ጨምሯል ተጠቃሚዎችስ?
የማሪዋና ችግር አካላዊ ከሆነው ባሻገር በሥነ ልቦና በኩልም በድብርት፣ በጭንቀትና በፍርሃት ስሜቶች ብቻ አይቆምም፣ ሱሱ እየበዛና እየቆየ ሲሄድ ግለሰቦቹ ራስን የመጥላትና ራስን የመግደል ሙከራ ውስጥ ይገባሉ (ራሱን ለመግደል ሙከራ የሚያደርግ ማንኛውም ሰው እርዳታ ካላገኘ ራሱን ማጥፋቱ የሚጠበቅ አደጋ ነው) ጥናቶች ተሰብስበው ማጠቃለያ (Review) ተዘጋጅቶላቸው በ2002 ለአሜሪካን ሴኔት የህግ ክፍል የቀረበ መረጃ (Physiological and effect of cannabis ለዚህ ፀሁፍ መነሻ ሆኗል፡፡ እንደውልላችሁ ለምትሉ አንባብያን 0115159126 ተጨማሪ ስልካችን ነው፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

ከአደገኛ አደንዛዥ ዕፆች ጋር ተያይዘው የሚደረጉ ወንጀሎችን በተመለከተ፣ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ቀውስ በማስከተላቸው ከአገርም አልፎ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕግ አወጣጥም ሆነ በክትትል ረገድ ትኩረት ሲስቡ ቢታይም
እነዚህ ወንጀሎች አሳሳቢ በሆኑበት ደረጃ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ በብቃት አልታቀፉም …” ይላል፡፡

   ከአንድ ሳምንት በፊት ከወዳጆቼ ጋር ምሳ በልተን ቡና እየጠጣን ሳለ የጀመርነው ጨዋታ ለዚህ ፅሑፍ መነሻ ሆነኝ፡፡ የጨዋታችን ርዕስ የነበረው እሁድ መጋቢት 14 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት  በኢ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ  የተላለፈው የ“ሰይፉ ፋንታሁን ሾው” ነው፡፡ በትዕይንቱ ላይ አርቲስት አለማየሁ ታደሰና ግሩም ኤርሚያስ እንዲሁም ኮሜዲያን ደረጄ ኃይሌ ተጋባዥ የነበሩ ሲሆን ወዳጃችን እነሱ የተናገሩትን ነገር እያስታወሰ ጥቂት አዝናናን፡፡ እጅግ የማደንቀው አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ተጋባዥ የነበረበትን ይህንን አዝናኝ ትዕይንት አለመከታተሌ ቢቆጨኝም በድጋሚ የሚተላለፍብትን ቀን ጠብቄ ትርዒቱን ለመከታተል እንድወስን ያደረገኝ ግን ወዳጄ ስለአርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ያወጋን ነገር ነበር፡፡ እናም መጋቢት 18 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት ትዕይንቱ በድጋሚ ሲተላለፍ ተመለከትኩት፡፡ አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ወደፊልም ኢንዱስትሪው ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ እያሳየ የመጣውን የትወና ብቃት ለትህትና ፍጆታ ሳይሆን እጅግ ከልብ የማደንቅ መሆኔን እየገለፅኩኝ ትዝብቴን እነሆ ላካፍላችሁ፡፡
አርቲስቱ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ የሆነ ሰውን ገፀ-ባህሪ ወክሎ ስለተወነበት “በጭስ ተደብቄ” የሚል ርዕስ ያለው አዲስ የቪዲዮ ፊልም ከሰይፉ ፋንታሁን ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው መልስ እሱ የሚከተለው የትወና ዘዴ “ሜተድ አክቲንግ” (method acting) የሚባለውን እንደሆነ ገልጿል፡፡ አክሎም በዚህ የትወና ዘዴ መሰረት ተዋናዩ የተሰጠውን ገፀ-ባሕሪ መስሎ ሳይሆን ሆኖ መገኘት ያለበት በመሆኑ፣ እሱም ገፀ-ባሕሪውን ለመሆን ብሎ ካናቢስ የተሰኘውን አደንዛዥ ዕፅ በፊልሙ ቀረፃ ወቅት ደጋግሞ እንደተጠቀመና በዕፁ ደንዝዞ አቅሉን በመሳቱ ትወናውን ለተወሰነ ደቂቃ ማከናወን እንዳልቻለ አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጠ፡፡ አርቲስቱ ካናቢስ ዕፅ አጭሶ መተወኑን በመግለፅ ብቻ አልተቆጠበም። በፊልሙ ቀረፃ ወቅት አርቲስቱ በዕፁ ደንዝዞ ከገባበት ሰመመን ሲነቃ፣ ከፊልሙ ባለሙያዎች ጋር ያደረገውን ንግግር ጭምር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አሳየን፡፡ አርቲስቱ ይህንን ማድረጉን መግለፅ በጀመረባት ቅፅበት አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ራሱን በመነቅነቅ ካሳየው አድንቆት ጀምሮ ተቀንጭቦ የታየው ፊልም ሲጠናቀቅ በስቱዲዮ ተመልካቾች እስከተቸረው ደማቅ የአድንቆት ጭብጨባ ድረስ ሙገሳን ሲቸረው አየሁ፡፡ የትወና ብቃቱን፣ ጥረቱን እና ቁርጠኝነቱን ደግሜ ባደንቀውም ይሄን ድርጊቱን ግን ለማሞካሸት እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም የአርቲስቱ ድርጊት ለተሳካ ትወና ከተደረገ ጥረት ባሻገር፣ በአገራችን የወንጀል ሕግ ቀላል የማይባል የእስራት ቅጣትን ሊያስከትል የሚችል የወንጀል ድርጊት ነው፡፡   
በተለየ ሁኔታ ካልገለፅኩት በቀር ከዚህ በኋላ የምጠቅሰው ሕግም ሆነ አናቅፆች አሁን በስራ ላይ ያለውን የ1996 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግን እና በውስጡ የተካተቱትን አናቅፆች እንደሆነ እየገለፅኩ፣ የአርቲስቱ ድርጊት ወንጀል ነው ያልኩበትን ምክንያት ልተንትን፡፡ የ1949ኙ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ከተሻሻለበት ምክንያቶች አንዱን ሕጉ በመግቢያው ላይ ሲገልፅ “… ከአደገኛ አደንዛዥ ዕፆች ጋር ተያይዘው የሚደረጉ ወንጀሎችን በተመለከተ፣ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ቀውስ በማስከተላቸው ከአገርም አልፎ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕግ አወጣጥም ሆነ በክትትል ረገድ ትኩረት ሲስቡ ቢታይም እነዚህ ወንጀሎች አሳሳቢ በሆኑበት ደረጃ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ በብቃት አልታቀፉም …” ይላል፡፡ በመሆኑም አሁን በስራ ላይ ያለው የወንጀል ሕግ፣ አደንዛዥ ዕፆች እያስከተሉት ያለውን ከፍተኛ ቀውስ ታሳቢ አድርጎ የወጣ ነው፡፡ በአንቀፅ 1 ሥር እንደተገለፀው የወንጀል ሕጉ ዓላማ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግስት፣ የህዝቦቿን፣ የነዋሪዎቿን ሰላም፣ ደህንነት፣ ስርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ በመሆኑ፣ የወንጀል ሕጉ በአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ላይ ጠበቅ ያለ ድንጋጌን ይዟል፡፡
አንድን በሕግ የተከለከለ ድርጊት ማድረግ ወይም በህግ የታዘዘውን አለማድረግ የሚያስቀጣው ሕገወጥነቱና አስቀጪነቱ በሕግ ሲደነገግ እንደሆነ አንቀፅ 23(1) ይደነግጋል፡፡ ለምሳሌ ጉቦ አልቀበልም ማለት ወንጀል ነው የሚል ድንጋጌ በወንጀል ሕጉም ይሁን በሌሎች ሕግጋት ወንጀል ነው ተብሎ የተደነገገ ባለመሆኑ፣ አንድ ሰው ጉቦ አልቀበልም ቢል አይቀጣም፡፡ አንቀፅ 23 (2) ደግሞ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ደግሞ ወንጀሉን የሚያቋቁሙት ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ በዚህ አንቀፅ አነጋገር ሕጋዊ ፍሬ ነገር የሚባሉት ለጉዳዩ አግባብነት ባለው አንቀፅ የተጠቀሱትን ዝርዝር ፍሬ ነገሮች መሟላት፣ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር የሚባለው በሕጉ እንዳይፈፀም የተከለከለን ድርጊት መፈፀም ወይም እንዲደረግ የታዘዘን ድርጊት አለመፈፀም እና ሞራላዊ ፍሬ ነገር የሚባለው ድርጊቱን የፈፀመው ሰው ድርጊቱን ሲፈጽም የነበረው የሃሳብ ክፍል መሟላቱ ማለትም በአንቀፅ 57 እንደተብራራው ድርጊቱን የፈፀመው አውቆ ወይም እንደሁኔታው በቸልተኝነት መሆኑ ነው፡፡ አንቀፅ 57(2) አንድ ሰው የወንጀል ድርጊት ቢፈፅምም ጥፋተኛ የማይሆነበትን ምክንያት ሲገልፅ “ማንም ሰው የፈፀመው ድርጊት በሕግ የሚያስቀጣ ቢሆንም ምንም ጥፋት ሳያደርግ ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ኃይል ምክንያት ወይም ድንገተኛ አጋጣሚ ነገር የተፈፀመ ወይም የደረሰ ሆኖ ሲገኝ በወንጀል ሕግ ሊፈረድበት አይገባውም” ይላል፡፡
ከዚህ በላይ የተገለፁትን የሕግ ድንጋጌዎች እንደመንደርደሪያ ይዤ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስ፡፡ ሕጉ በርዕስ ስምንት ሥር በጤና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን የዘረዘረ ሲሆን በዚሁ ርዕስ ምዕራፍ አንድ ክፍል ሁለት ስር፣ በሰውና በእንስሳ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮችን በማምረትና በማሰራጨት የሚደረጉ ወንጀሎች ተዘርዝረዋል፡፡ በአንቀፅ 525 ሥር የተደነገገው መርዛማ ወይም የናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ መድሐኒቶችን ወይም ዕፆችን ማምረት፣ መስራት፣ ማዘዋወር ወይም መጠቀም ከእነዚህ የወንጀል ድርጊቶች አንዱ ሲሆን አሁን ለያዝነው ጉዳይ ተገቢነት አለው፡፡ አንቀፅ 525 ስድስት ንዑሳን አንቀፆችን የያዘ ሲሆን በንዑስ አንቀፅ (4)(ለ) ሥር የሚከተለው ተደንግጓል፡-
“ማንም ሰው…ከእነዚህ ነገሮች በአንዱ ያለሐኪም ፈቃድ ወይም በማናቸውም ሌላ ሕገወጥ መንገድ የተጠቀመ ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀምባቸው ያደረገ፤ እንደሆነ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከሃምሳ ሺህ በማይበልጥ መቀጫ ይቀጣል።” (ያሰመርኩባቸውን ቃላት ልብ ይበሉ)
ሕጉ “ከእነዚህ ነገሮች” የሚለው በንዑስ አንቀፅ 1 የተገለፁትን መርዛማ ወይም የናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ መድሐኒቶችን ወይም ዕፆችን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
የካናቢስ ዕፅ ይዘው፣ ሲሸጡ፣ ሲጠቀሙ ወዘተ ተይዘዋል ተብለው በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ የወንጀል ምርመራ ሲጣራ ከሚፈፀሙ ነገሮች አንዱ የካናቢስ ዕፅ የተባለውን ነገር በላብራቶሪ ማስመርመር ነው። በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ለሚመለከታቸው አካላት በሚሰጠው የላብራቶሪ ምርመራ ውጤት የሚከተለውን ውጤት ይገልፃል፡፡ “የካናቢስ ዕፅ ሰዎችን ሱስ በማስያዝ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መንስኤ እንዲሆኑ ስለሚገፋፋ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወር እና በጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደ ዕፅ ነው፡፡” ይህ የውጤት መግለጫ እና የአንቀፅ 525(1) እና (4) አገላለፅ የካናቢስ ዕፅ ማንም ሰው እንዲጠቀምበት የማይፈቀድ እና ጥቅም ላይ ከዋለም ተጠቃሚውን የሚያስቀጣው እንደሆነ ለመደምድም ያስችለናል፡፡
ካናቢሱን ማጨሱ “የተጠቀመ” የሚለውን እና ካናቢስን መጠቀም በሕግ የተከለከለ መሆኑና ዕፁን የተጠቀመው ለሕክምና ዓላማ አለመሆኑ “ያለሐኪም ፈቃድ” ወይም “በማናቸውም ሌላ ሕገወጥ መንገድ” የሚለውን የሕጉን ፍሬ ነገሮች የተሟሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ካናቢሱ አደንዛዥ መሆኑን እያወቀ ይህንኑ ውጤት ለማግኘት ፈልጎ መጠቀሙ የህጉን ሞራላዊ ፍሬ ነገር የተሟላ ያደርገዋል፡፡ ካናቢስ ማጨሱ ደግሞ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ያሟላል። ዕፁን የተጠቀመው ምንም ጥፋት ሳያደርግ ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ኃይል ምክንያት ወይም ድንገተኛ አጋጣሚ ባለመሆኑ የአንቀፅ 23(1) እና (2) እና 525(4)(ለ) አነጋገር የአርቲስቱን ድርጊት በሕግ የሚያስቀጣ የወንጀል ድርጊት ያደርገዋል፡፡
እዚህ ጋር አንባቢያን ሊያነሱት ከሚችሉት ዋነኛ ጥያቄ አንዱ አርቲስቱ ካናቢስ ያጨሰው ለሥነ-ጥበብ ሥራ እንጂ ሌሎች የዕፁ ተጠቃሚዎች እንደሚያደርጉት በዕፁ ለመደሰት ስላልሆነ እንዴት ወንጀል ይሆናል? የሚል እንደሚሆን እገምታለው። ሕጉ ለሥነ-ጥበብ ዓላማ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀምን ይፈቅዳል ወይ? ወደ መልሱ ከመሄዴ በፊት አንድ የሕግ አቀራረፅ ሥርዓትን ላንሳ፡፡ ሕጎች ጠቅላላ ድንጋጌ እና ልዩ ድንጋጌ በሚል ሥርዓት ሊቀረፁ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ከአንቀፅ 546 እስከ 549 ባሉት ድንጋጌዎች መሰረት ፅንስ ማቋረጥ ወንጀል መሆኑ ጠቅላላ ድንጋጌ ነው፡፡ ነገር ግን በአንቀፅ 55 1(1) (ሀ) መሰረት በመደፈሯ ምክንያት ወይም ከዘመዷ ጋር በተደረገ የግብረ ስጋ ግንኙነት የፀነሰች ሴት ፅንስ ብታቋርጥ በወንጀል እንደማያስቀጣት መደንገጉ ልዩ ድንጋጌ ነው፡፡ ስለዚህ ልዩ ድንጋጌው የተሟላ ከሆነ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ከዚህ የሕግ አቀራረፅ ሥርዓት አንፃር የያዝነውን ጉዳይ ሥንመለከተው፣ ከሕክምና ዓላማ ውጪ መርዛማ ወይም የናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ መድሐኒቶችን ወይም ዕፆችን ለመጠቀም የሚቻልበት አንዳችም ልዩ ሁኔታ በሕጉ ባለመቀመጡ ካናቢስን ለፊልም ቀረፃ በሚል ሰበብ ማጨስ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ወንጀል ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም፡፡
ድርጊቱ በወንጀልነት ከተፈረጀ በስተመጨረሻ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ይህ የወንጀል ድርጊት በማን እና እንዴት ምርመራ ይካሄድበታል? የሚለው ነው፡፡ ማንም ሰው ወንጀል ሲሰራ ያየ ወይም ያላየም ቢሆን የወንጀል ክስ እንዲቀርብ ወንጀሉን ለማስታወቅ መብት እንዳለውና ጠቋሚው ሳይታወቅ (በስልክ፣ በፖስታ ወዘተ) ለፖሊስ ጥቆማ ከደረሰ ደግሞ ፖሊስ ወንጀል ስለመሰራቱ በአካባቢ ሁኔታ የተደገፈና የሚታመን ሆኖ ከተገኘ፣ በፖሊስ ምርመራ እንደሚደረግ በ1954 ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀፅ 11(1) እና 12 ሥር ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም አርቲስቱ የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን በአደባባይ በመግለፁ፣ ወንጀል ስለመሰራቱ እንዲታመን የሚያስችል በመሆኑ፣ ፖሊስ በራሱ ተነሳሽነት አልያም የወንጀል ድርጊቱ ስለመፈፀሙ አውቃለው የሚል ሰው ጥቆማ ካቀረበ፣ ጥቆማውን መሰረት አድርጎ የምርመራ ሥራውን ለመጀመር ሥልጣን አለው፡፡ በዚህም መሰረት የተከሳሹ እና የፊልም ሥራውን የሰራው ድርጅት የመኖሪያ አድራሻ አዲስ አበባ ከመሆኑ አንፃር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተከሳሹን በሕግ አግባብ ይዞ ምርመራ መጀመር ይችላል፡፡ የምርመራ መዝገብ የሚጣራው ወንጀሉ በተፈፀመበት ሥፍራ ባለ ፖሊስ በመሆኑ የፊልም ቀረፃው የተካሄደበትን ቦታ በምርመራ ለይቶ፣ የፊልሙ ቀረፃ የተካሄደበት ቦታ ለሚገኘው የፖሊስ ተቋም ጅምር የምርመራ መዝገቡን በመላክ ጉዳዩን በጥልቀት አጣርቶ፣ የቴሌቪዥኑን ሥርጭት ጨምሮ ወንጀሉ ስለመፈፀሙ የሚያስረዱ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ፣ ጉዳዩን ለሚመለከተው ለፌደራል ዓቃቤ ሕግ በማቅረብ በምርመራ መዝገቡ ላይ ለማስወሰን ስልጣን አለው፡፡
አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ በትዕይንቱ ላይ እንደገለፀልን “በጭስ ተደብቄ” በሚለው ፊልሙ አደንዛዥ ዕፅ በተጠቃሚዎቹ ላይ የሚያደርሰውን ሁለገብ ቀውስ፣ የሱሰኞቹን ሕይወት ቁልጭ አድርጎ በመተወን ሊያሳውቀንና ሊያስተምረን የተነሳ መሆኑ እጅጉን ሊያስመሰግነው የሚገባ ቢሆንም የፈፀመውን ድርጊት ወንጀልነት ባለማወቅ፣ ባለማስተዋል ወይም በመዘንጋት ጉዳዩን በድፍረት ለአደባባይ ማቅረቡ ግን አንድ ትምህርት የሚሰጠን ይመስለኛል፡፡ ይህም በሕጉ አንቀፅ 81(1) የተደነገገው “ህግን አለማወቅ ወይም በሕግ ላይ መሳሳት መከላከያ ሊሆን አይችልም” የሚለው ነው፡፡ የዚህ ፅሑፍ ዓላማም ይህንኑ ማስገንዘብ ነው፡፡ ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንምና በቀናነት የምንፈፅማቸው ድርጊቶች ሕግን የተከተሉ መሆናቸውን ለማወቅ ይረዳን ዘንድ የህግ ዕውቀታችንን ለመገንባት ልቦናችንን እንክፈት፡፡ ብሩሕ ቀናትን እመኝላችኋለሁ፡፡ ሰላም!!
ፀሐፊውን በሚከተለው ኢሜይል አድራሻቸው ማግኘት ይችላሉ፡፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Published in ጥበብ
Monday, 14 April 2014 10:17

የትሮይ ፈረስ

ምን ዓይነት ዕዳ ነው እባካችሁ?!
አንዳንዴ ደሞ ከአብሮነቱ ጊዜ እጅግ በላቀ አኳኋን ትዝታው የሚጣፍጥ ፍቅር አለ፡፡
በሰለጠኑ ጥንዶች ወግ “ይብቃን …. አይደል?” ተባብለን በጨዋ ደንብ በቅርቡ የተለየኋት የዓመታት ፍቅረኛዬ ለካንስ ያኔ አልታወቀኝ ኖሮ እንጂ ካሉት ሁሉ የተሻለች ኖራ መርሳቱ ላይ ትንሽ አወከኝ፡፡
አይ …፣ ልመን - ምናባቱ፡፡ ቆጭቶኛል፡፡
ከዚያ ወዲህ “የሚያክለኝ አጣሁ!” ብዬ ራሴን እዚያ ላይ ኮፈስኩና ሥራ ሥራዬን ብቻ መከታተል ዓላማዬ አደረግሁ፡፡
ነገር ግን በየት በኩል?
የኔ ነጠላ መሆን ለፍቅር ሕይወታቸው ብርቱ አደጋ እንደሆነ የሰጉ ይመስል እኔን የሴት ጓደኛ ለማስያዝ ባልንጀሮቼ ተማማሉብኝ፡፡
ተቀምጬ ደህና ሂሳቤን ከምቀምርበት ዴስክ አንዷን ማቶት ፊት አምጥቶ ያሳየኝና “እ…? እንዴት ናት?” ይለኛል፡፡ “… ምንም አትል፣” እለዋለሁ “አይ ሰው!” እያልኩ በልቤ፡፡ ወየው ጉድ! ለራሱ እንደ ሱፍ አበባ የደመቀች ውብ ልጅ መርጦ ይዞ ሲያበቃ፣ ለኔ ይቺ ጣቷ አጫጭሩን ሙዝ የመሰለ ጦጣ ያጨልኝ ከቶ እንዴት ቢገምተኝ ይሆን?
ደሞ ሌላዋን አመጡ፡፡ “ተውኝ፣ ይቅርብኝ …. አይሆንም!” ብዬ ተቃውሞየን ባስመዘግብም “ምን ቸገረህ ለትንሽ ጊዜ አጥናት፣” ብለው ሐይ ሐይ አሉኝና ጥናቱን ጀመርኩ፡፡ እውነት እውነት ነው የምላችሁ … እንደዚያ ያለ ውድ Feasibility Study ከሰሐራ በስተደቡብ ተካሂዶ አያውቅም፡፡ ልጅቷ አሥራ አምስት ቀን በማይሞላ ጊዜ ውስይ ከቆንጆ ልጅነት አጭር ቀሚስ ወደ ለበሰ ተንቀሳቃሽ Cost Centernet ተቀይራ ትታየኝ ጀመር፡፡
ሸሸሁ፡፡
እንባዬን የተመለከቱ ጓደኞቼ በሐዘኔታ የአጭር ጊዜ ፋታ ሰጡኝ፡፡
ጥቂት ሰነባብተው ተመለሱብኝ፡፡
ያ ሚካኤል ነው ዛሬ በጠዋቱ የመጣው፣ “… ኋላ ምሳ አብረን ነን፣” አለኝ “ሌላ ሰው አያስፈልግም፡፡ የማናግርህ ነገር አለ!”
ቀና አልኩና አየሁት፡፡ የእፎይታ ጊዜዬ እንደተፈፀመ ታውቆኛል፡፡ ቢሆንም ያለ ሙግት እጄን ላለመስጠት ስል “… ልብ አርግ፣ የጋብቻ ሕይወቴን በተመለከተ ምንም ዓይነት ውይይት አናካሂድም፣” አልኩት ኮስተር ብዬ፡፡
ለጥቂት ሰከንዶች ያህል በተመስጦ በዝምታ አስተዋለኝና ሄደ፡፡
ምሣ ቀርቧል፡፡ እምጵ - አቤት ዓሣ! ከክሣቱና የመጣመሙ የሌሊት ወፍ እንጂ ምኑም ዓሣ አይመስል፡፡ ክክ ወጡም እንደ ግሎብ ተድቦልቡሎ ለእንጀራው መሃል አለ፡፡ የአንዱ አተር ክክ ስፋት ከዲስክ አይተናነስም፡፡
“ብላ እንጂ!” አለኝ ሚካኤል ምግቡን እንደ ጸጉረ-ልውጥ ፍጡር በመገረም ሳጤነው ተመለከተና፡፡ ወጡ የዘንድሮ ለመሆኑ ለጌታ ፀሎቴን እያደረስኩ ጀመርኩት፡፡ እርቦኝ ነበር፡፡
እሱም አተሩን አፉ ውስጥ ለመፈርከስ ያመቸው ዘንድ ፊቱን ቁልቁልና ሽቅብ እያረዘመ ስለ አዲሷ ልጅ ያወጋኝ ጀመረ…
“አበጋዝ..፣” አለኝ ገና ሲጀምር፣ የጉዳዩን ክብደት ለማስረገጥ ሲባል ከወትሮው ወፈር በተደረገ ድምፅ፤፣ “”አበጋዝ-ፍቅር ይዞህ ያውቃል?”
“አዬ፣ የዛሬውስ - ፍልስፍና ቅልቅል ነው!” እያልኩ በልቤ፣ “አዎን” ስል መለስኩለት፡፡
“ፍቅር ስልህ … ‘አልይህ!’ እየተባልክ ሄደህ ልጅቷ ፊት ጧት ማታ የተገተርክበት? ‘አልፈልግህም!’ እየተባልክ ደርዘን ባለ ሁለት ገጽ ደብዳቤ የፃፍክበትን? ሌላዋ ከምትስምህ እሷ ብትገላምጥህ የመረጥክበት … ?”
እያቅማማሁ አቋረጥኩት፣ “እኔ እንጃ!” ግር እያለኝ፣ “እንደሱ እንኳ እኔ እንጃ …፤”
“በትካዜ ብዛት ቀልድ አላስቅህ፣ እህል አልበላልህ …፤”
“አአይ፣” አልኩት አሁን እርግጠኛ ሆኜ፣ “እንደ እሱ አይነቱ እንኳን … አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ እኔ ሆዴን ቢያመኝም እንኳን እህል እንቢ አይለኝም። ጥሩ አድርጎ ይበላልኛል፡፡ ሆሆሆይ! ደግሞ ጨጓራና ፍቅር ምን አገናኛቸው?” እያልኩ ጮክ ብዬ ተገረምኩ፡፡
ሚካኤል በትንሹ እየፈገገ ንግግሩን ቀጠለ፣ “ይኸውልህ አበጋዝ፣ አንድ እንዲህ አሁን እንዳልኩህ የምወዳት ልጅ ነበረችኝ፡፡ የመልንኳና የቁመቷን፣ የአይኗንና የጥርስዋን ካለየሀት በቀር እንኳንስ በእኔ ጎልዳፋ ንግግር በዳቪንቺ የስዕል ችሎታም ሊገለጽ የሚቻል አይደለም…፡፡”
“የሥላሴ ያለህ!” አልኩና አቋረጥኩት፣” “አደራህን…፣ መቸም - ስለ ማርሊን ሞንሮ አይደለም የምታወራው!” አልኩት በተጠቀመው የውበት አገላለጽ በዕውነት ደንግጬ፡፡
“አትቀልድ!” አለኝ ድንገት ዓይኑ እንባ አቅርሮ እያብረቀረቀ፣ “አትቀልድ”
ከዚያጥቂት ፀጥ ብሎ ቆየና “እንዴት እወዳት ነበር መሰለህ!? እንዴት!”
“ታዲያ ምን ሆነች? አገባች? ውጪ ሄደች? ወይስ … ሞተች? መቸም ከዚህ አያልፍም፡፡”
“አለች …፣ እንደውም ከእዚህ ከኛ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ያለው የጉዞ ወኪል ቢሮ ነው የምትሰራው፤”
“እና?”
“እናማ … በአጭሩ ልጅቷ አውሬ ነች፡፡ “እንቢ” የምትልህ አንተን ስለምትወድህ ወይም ስለምትጠላህ አይደለም እንዲሁ ወንድ ስለምትፀየፍ ይመስለኛል፡፡ ቃሉ በ“መፀየፍ” ነው፡፡ በኋላ እንደ ደረስኩበት አባቷ፣ እናቷን ክፉኛ ያሰቃያት ነበር አሉ። ያለ መጠን ቀናተና፣ ጠጪና ተደባዳቢ፡፡ ሲነሳበት ጉማሬና ካራ ይዞ በውድቅት ሉሊት ቀበሌ ግቢ ድረስ ነበር የሚያሯሩጣት - ዕርቃኗን! አሁን ተፋተዋል፡፡ ያልኩህ ልጅ ከእናትዋ ጋር ብቻዋን ነው የምትኖር፤ እና ለዚህ ይመስለኛል አይደለም ወንድ፣ ሴት እንኳን እንደ አውሬ ነው የምትሸሸው፡፡ ከአንድ ሴት ጓደኛዋ በቀር ከሌላ ጋር አትታይም፡፡ ፈፅሞ! የጓደኛዋ መልክ ደግሞ አስቀያሚነቱ ከሷ ቁንጅና በእጥፍ ስለሚልቅ ማንም አይጠጋትም…”
እንደ ምንም ብዬ ጣልቃ ገባሁና አቋረጥኩት፣ “… ይኸውልህ… ሚካኤል፣ ስላሰብክልኝ ከልብ አመሰግንሃለሁ፡፡ ነገር ግን … እኔ የአባቷን ዕዳ ለሷ የምከፍልበት አቅሙም ፍላጎቱም የለኝም፡፡ ምሳችንን አብቅተናል - እንሂድ፡፡” ድምፄ የመጨረሻ ነበር፡፡
“እሺ .. ይሁን፣” አለኝ፡፡ “ግን - አንዴ ብቻ እግሯን እየው፡፡ እግር እንደ ምትወድ አውቃለሁ። አንዴ ብቻ እግሯን እየውና የቀረው .. ያንተ ፈንታ ነው፡፡”
እግር … በእርግጥ እወዳለሁ፡፡ ከሴት ልጅ ውበት ከቶ ምንም ቢሆን ዕድሜ የማያደበዝዛቸው ረዥም ቁመናና ያማረ ቅርፅ ያለው እግር ናቸው፡፡ እና … እኔም በስተርጅና ዘመኔ ለዓይኔ ማረፊያም መፅናኛም ይሆነኝ ዘንድ የማገባት ልጅ እነዚህን ሁለት ነገሮች ታሟላ ዘንድ የግድ ነው፡፡
“እእእ…፣ እስኪ፣” አልኩ፡፡
ሚካኤል ይስቅብኝ ጀመር፡፡
አዲሱን ሐሳቤን የሰሙ ጓደኞቼ “Kamikaze Pilot” በሚል ስም ይጠሩኝ ጀምረዋል፡፡ የዚያችን ሴት - ነብር የሆነች ልጅ ዝና ሁሉም ያውቃሉ፡፡ ለካስ እኔ ለረዥም ጊዜ ትዳር-አከል በሆነ ጥሩ ፍቅር ውስጥ ስለቆየሁ ኖሯል እንጂ ከሁሉም ጓደኞቼ የልጅቷን የግርፊያ ወላፈን ያልቀመሰ አልነበረም፡፡
“ዋ…! አርፈህ ብትቀመጥ ይሻልሀል፡፡ ቀዳድዳ ነው የምትጥልህ!” ይሉኛል ቢሮ ውስጥ ተሰብስበው እየሳቁ፡፡
ሚካኤልን ያልተቀየመ የኔ የቅርብ ወዳጅ አንድም አልተገኘም፡፡ “እንዴት! እንዴት ዓይንህ እያየ ይህንን የዋህ ልጅ ወስደህ ሳማ ላይ ታስተኛዋለህ?!” ይሉታል፡፡
እርጉም እልህ ያዘኝ፡፡
በዚያ ላይ … እግሯ ደሞ! እግሯ… ደግሞ! እግሯ!!!! ሰአሊ ለነ ቅድስት!
ሐቁን ልናገር አይደል? እህል … እንደ ድሮው አልበላ ብሎኛል፡፡
እኔ እንጃ!
ዕቅዴን በጥበብና በማስተዋል አሰናዳሁ፡፡
ማንንም ምስጢረኛ አላረግሁም - ከልቤ በቀር። የልጅቷ አንድና፣ አንድ ደካማ ጎን ያቺ በአሳዛኝ ሁኔታ መልከ ጥፉ የሆነች ባልንጀራዋ ብቻ ነበረች፡፡
ዕቅዴ በሚገባ ተጠንቶ ከተጠናቀቀ በኋላ አጭር ፀሎት አድርሼበት ተንቀሳቀስኩ - “አምላኬ ሆይ! ይቺን ልጅ የዘላለም ዕርስት አድርገህ ስጠኝ….”
ቢሮዋ ስገባ ደንበኛ እያስተናገደች ስለነበር የእንግዳ ማረፊያው ላይ ሄጄ ተቀመጥኩ፡፡
ቢሮው ሰፊ፣ እጅግ ዘመናዊ፣ ንፁህ እና የሚያምር ነው፡፡ በዚያ ላይ የውጪውን የሚፋጅ አየር በምን ውጪ እንዳስቀሩት አላውቅም - ቀዝቃዛ ነበር፡፡ በግማሽ ክብ ቅርጽ ከተሰራ ረዥም ዴስክ ጀርባ ብዙ ሆነው በፀጥታ ይሰራሉ፡፡
ሰውየውን አስተናግዳ እንደ ጨረሰች ሄድኩና ጠረጴዛዋ ጋ ተቀመጥሁ፡፡ አቤት ፊቷ - አለት ማት አይደል እንዴ! ምንም ነገር አይነበብበትም፡፡ “ምን ነበር?” እንኳን አላለችኝም፡፡ ዝም ብላ ጣቶቿን ኮምፒውተሩ መደገፊያ ላይ አሳርፋ ትጠብቀኛለች፡፡
“… አይ … የግል ጉዳይ ላናግርሽ ነበር፣” ከማለቴ
እግዚኦ!
ይህስ - እውነትም የበሽታ ነው፡፡
በአፍታ ድሮም ቀጥ ብሎ የነበረው ከወገቧ ላይ ያለው አካሏ እንደ ኮብራ ዕባብ ሆኖ ቀጥ አለ። ከዚያም ዛር እንደ ያዘው ሁሉ ሰውነቷን አንድ ጊዜ በብርቱ ሰበቃትና ቀይ ፊቷ የበሰለ እንጆሪ መስሎ ተቀጣጠለ፡፡ አስከትላ በጎላ ድምጽ መዓቱን ልታወርድብኝ ስትሽቀዳደም ቶሎ በመጣደፍ “… ጓደኛሽን እንድታማልጅኝ ነበር፣” አልኳት በተሰበረ ድምጽ፣ በታሪክ የመጨረሻው ግሩም በሆነ ትህትና።
የኮብራው ምላስ ስርቅርቅ የሕንድ ዘፈን የሰማ ያክል ከመቅፅበት ወደ ሰገባው ተከተተ…
ዛሬ ቅዳሜ እሷን እየጠበቅሁ ነው፡፡ ሁነኛ ቀጠሮ አለን፡፡
ያን እለት እንዴት ደስ ተሰኝታለች! በዚያ ላይ ገርሟትም አላባራ፡፡ ምክንያቱም - ይኸውና ለውድ አስቀያሚ ጓደኛዋ በመጨረሻ የወንድ ጓደኛ ተገኝቷልና ነው፡፡
መጣች፡፡
እስከ አሁን ዕቅዴ ሁሉ እንደ ታሰበው ያለ እንከን እየተሳካ ቢሆንም አሁን አንድ ግዙፍና አስቸጋሪ መሰናክል ተጋርጦብኛል፡፡
ዓይኔ፡፡
ከንፈርና እግሯ ላይ ሳፈጥ ብትይዘኝ በነዚያ አለንጋ ጣቶቿ ሁለቴ በጥፊ ገርፋ ስታበቃ እንዳታባርረኝ እጅግ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረብኝ፡፡
እኔ ጋ መጥታ ተቀመጠች፡፡ (በህይወቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም) ፈገግ ብላ ነበር።
ገና ካሁኑ ሴቱም ወንዱም በቅናት አይን ያየኝ ጀምሯል፡፡
“እንደምን ነሽ?” አልኳት፣ ከማክበር ጋር፡፡
“አለን፣” አለችኝ፡፡ በሚደንቅ ሁኔታ ነፃ ሁና ነበር የምታዋራኝ፡፡
“ማን ነው ስምሽ?”
“ልያ፣”
ሻይ ቡና ቀርቦልናል፡፡
“ይኸውልሽ ልያ…፣ ጓደኛሽን በጣም እወዳታለሁ፡፡ በቁም ነገር…፣”
ዓይኗን እንባ አቅርሮ አቋረጠችኝ፣ “ፅጌ እኮ እንዴት አይነት ሰው መሰለችህ! ወይኔ እኮ - ውስጧ ሲያምር! እንዴት ዕድለኛ ልጅ እንደሆንክ ብታውቅ!”
“ዝም በይ - ሰባኪ!” አልኳጽ በሆዴ፡፡ የጓደኛዋ አፍንጫ እኮ ዝናብ ያስገባል፡፡ ልፊ ቢላት ነው እንጂ ፅጌን እንደሆነ “የወርቅ እንቁላል ትወልዳለች” ቢሉትም አይሁድ እንኳን አይነካትም፡፡
ሆኖም ግን በፍቅር ፍላፃ እንደተወጋ አፍቃሪ ሁሉ ገጽታዬን ማደካከሜ አልቀረም፡፡
“እሱንማ አውቄኮ ነው፡፡ የአክስቴ ልጅ አብራችሁ ኮሜርስ ትማር ነበርና …፣”
“ማን?” አለችኝ ፊቷ ሁሉ በፈገግታ እየሞቀ፡፡
“አታውቂያትም፣ የምትታወቅ ዓይነት ልጅ አይደለችም፡፡ ጭምት ነገር ነች …”
“ሳባ?”
“እንዴ! እንዴት አወቅሽ?” አልኩ የተደነቀ መስዬ፡፡ እኔ እኮ ከመጽሐፍ ቅዱሷ በስተቀር ሳባ የምትባል ልጅ በሕይወቴ አላውቅም፡፡
“እና … እባክሽን ልያ፣ በራሴ መንገድ ልቀርባት ሞክሬ ሁሌ አንድ ላይ ስለምትሆኑብኝ አልቻልኩም። ከሉሉ በፊት አንድ ነገር ግልጽ እንዲሆንልሽ እፈልጋለሁ፡፡ ከእሷ ጋር እስከ ሕይወቴ መጨረሻ ድረስ አብሬ መሆን የምፈልግ ሰው ነኝ፡፡ በዚያ ላይ ካንቺ ቃል እንደማትወጣ ሳባ ነግራኛለች። ስለዚህ ነገሩ እንደ ማይበላሽ እርግጠኛ ለመሆን ስል ነው አስቀድሜ አንቺ ዘንድ ልመና የመጣሁት። እኔ ምንም ነገር አይደለም የምጠይቀው፡፡ ልታይ!! መጀመሪያ አንቺ ለጥቂት ሳምንታት እይኝ፡፡ ከዚያ አንድ ላይ እዩኝ… እና ወስኑ፡፡” አቤት የድምፄ መለስለስ! የዓይኔ መቅለስለስ!
“እሱ ችግር የለዉም! ግን … በእናትህ እንዳትጎዳት! በእናትህ …፣” አለችኝ ዓይኖቿ ወፍራም እንባ አቅርረው፡፡
“ለማንኛውም፣” አልኳት፣ “… ለማንኛውም አንቺ አይተሽኝ አንድ ውሳኔ ላይ እስክትደርሺ ጉዳዩን በምስጢር ብትይዥው…፣”
አሁን እሷ ነች ጧትና ማታ የምትደውልልኝ፡፡ እጅግ ለምታፈቅራት ጓደኛዋ “ሸበላ” ባል ተገኝቷልና ነው እንዲህ እንቅልፍ ያጣችው፡፡
በየጊዜው እየተገናኘን መጨዋወቱን ተያይዘነዋል፡፡
“ግን …፣ እንዴት እንዲህ ልትወዳት ቻልክ?” ትለኛለች፡፡
“ምን መሰለሽ ልያ፣” እላታለሁ፣ “… ለትዳር ለትዳር እኮ እንደ እሷ ውበታቸው ትንሽ ከተት ያለ ቆንጆዎች ናቸው ጥሩ፣፡፡
በመገረምና በመደነቅ አፍ አፌን ታየኛለች - ‘እንዴት ያለ ብልህ ነው!’ በሚል አኳኋን፡፡
“እንዴ - ‘ቆንጆ ነን’፣ ‘የተማርን ነን!’ የሚሉትማ ፍዳሽን ነው የሚያስቆጥሩሽ፡፡ ትዳር ሳይሆን ከአንቺ ጋ ፉክክር ነው የሚገቡት፡፡ ልጅ ጡት አጥቢ ስትያቸው እንኳ አንተስ ሊሉሽ ምንም አይቀራቸውም! ምኔን አጠባለሁ?”
የሳቀችው … ሳቅ!
አንዳንዴ ደሞ ዕልም ብዬ እጠፋባታለሁ፡፡
ቢሮ ድረስ ፍለጋ የመጣች ዕለት በድንጋጤ አፋቸው በሀይለኛው የተላቀቀ ጓደኞቼ፣ ዛሬ ድረስ በትክክል መልሶ አልገጠመም፡፡
ሀይለኛ ቅናትና ክብር አድሮባቸዋል፡፡
“ለምን ጠፋህ?” አለችኝ እኔን እጅግ ደስ ባሰኘ ቅሬታ፡፡
ውበቷ ትንፋሽ ያሳጥራል፡፡
“ምን እባክሽ፣ ትንሽ ስራ ብጤ በዝቶብኝ ነው፡፡ በዚያ ላይ ፈተናውም ደርሷል…፣”፡፡
“የምን ፈተና?”
“አልነገርኩሽም እንዴ … ዩኒቨርሲቲ እየተማርኩ ነው እኮ…፣” አልኳት አቃልዬ፡፡
“እንዴት - በዲግሪ ተመርቄያለሁ አላልከኝም ነበር?” አለችኝ - ‘አንተ ቀጣፊ፣ ያዝኩህ!’ በሚል ቃና፡፡
“እሱማ … አዎ፣ ጨርሻለሁ፡፡ ግን … ማታ ማታ ድራፍት ከምጠጣ ብዬ እንደ ቀልድ ዩኒቨርሲቲ ጀመርኩና ዘንድሮ እመረቃለሁ፡፡”
ደነገጠች፣ “ወይኔ … ታድለህ! ሁለት ዲግሪ!”
“ምን … ይደረግ ብለሽ ነው፣” ራሴን ዓይን አፋርነትና ትህትና በተመላው አኳኋን አከክ አከክ አደረግሁ፡፡
የማናወራው ነገር አልነበረም፡፡ ቅራቅንቦ ነገር ሁሉ፡፡
“መጀመሪያ ሴት ነው ወንድ መውለድ የምትፈልገው?”
“ሴት፣”
“እንዴ - ለምን?” ትለኛለች፡፡
“ለምን እንደሆነ አላቅም፡፡ ግን ከመጀመሪያ ሴት ልጄ ጋር በጣም የቅርብ ጓደኛ የምንሆን ይመስለኛል። ለምሳሌ ቤት የተሰራው እራት ባያምረን እኔና እሷ ብቻ ተጠቃቅሰን ቀስ ብለን … ውጪ በልተን እንዳልቀመሰ ሰው የምንመለስ…. ምናምን፡፡ ብቻ … እንጃ እንደዚህ እንደዚህ ዓይነት ከሴት ልጄ ጋ ይታየኛል፡፡”
ዓይኗ ቅዝዝ እንደ ማለት ብሎ ታየኝ ጀመር፡፡
“እሺ ግን …፣ አያምስልብህና ፅጌ ‘አልፈልግም’ ብላ ድርቅ ብትል ምን ታረጋለህ?” አለችኝ አንድ ቀን፡፡
“እህ…! ምን አደርጋለሁ! እያዘንኩ፣ እየከፋኝ ይቀራል እንጂ፡፡ እንዴ - እኔ እሷን የመምረጥ መብት ያለኝን ያክል እሷም እኔን ያለመምረጥ መብት አላት እኮ!”
በእንዴት ያለ ከፍተኛ መገረምና አድናቆት እንዳስተዋለችኝ!    
“እሺ … ቆይ፣ ከተጋባችሁ በኋላ ብታናድድህስ?”
“እህ - እሱማ ያለ ነው እኮ!”
“አትቀጠቅጣትም?” ድንገት የእልህ እንባ በዓይኗ ሳይሆን በአፍንጫዋ በኩል መጣ፡፡
“አልገባኝም?!” አልኳት ፍፁም የተደናገርኩ በመምሰል፣ “እንዴት? ዱላ - ዱላ? እጄን አንስቼ?” ክፉኛ ግር እንዳለው ሰው ቅንድቦቼን አርገበገብኩ። “እንዴ ሚስቴ እኮ ናት - ግማሽ አካሌ፡፡ ለዛውም የተሻለው ግማሽ፡፡ እና - እንዴት ነው ራሴን የምመታው?”
አሁን ደሞ እሷን ግር አላት - የእውነት፡፡
“እስኪ … እግዚአብሔር ልክ እንደ ሰለሞን ሁሉ አንድ ነገር ብቻ ለምነኝ ቢልህ ምን ትጠይቀዋለህ?”
“መልካም ሚስት!” አልኳት፡፡
“አይ አንተ ደሞ!” አለችኝ እየሳቀች፣ “አይዞህ የፅጌን ፈተና እንደሁ ታልፋለህ፡፡ አታስብ፡፡ አሁን ጥያቄዬን በትክክል መልስ፣” ትላለች እያሾፈች፡፡
“ሙች እውነቴን እኮ ነው” እላታለሁ “እኔ ሀብት፣ ስልጣን፣ ዕውቀት … ለፍቼ፣ ደክሜ ላገኝ እችላለሁ ስል አስባለሁ፡፡ መልካም ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የምትገኝ ስጦታ ነች። በዚያ ላይ የተባረከች ሚስት ካለችኝ ሁሉ ነገር ይሳካልኛል፡፡ ምክንያቱም - እሷን ደስ ለማሰኘት ሌት ከቀን ነው የምሰራው፡፡ ጨቅጫቃ ነገር ከሆነች ግን የያዝሽው እንኴን ያመልጥሻል…፣
“አዎ፣” አለች በመስማማት ራስዋን እየነቀነቀች፣ … “ከእያንዳንዱ የተሳካለት ወንድ ጀርባ አንድ ሴት አለች ይባል የለ…፣”
“ከብዙ ያልተሳካለት ወንድ ጀርባም አንድ ሴት አለች፣” አልኳት፡፡
እንደ ፈላስፋ ልታየኝ ጀምራለች፡፡
ምሳሌ ሺ ዘመን ይንገስና ልጅትዋስ ወጥመዴ ውስጥ እየገባች ነው…
በቀን አንዴ ሳንገናኝ ከዋልን ቅር ይላት ጀምሯል። በምንም ተዓምር የማልቀይረውን በሳምንት አንድ ግዜ ብቻዬን ወደ ሲኒማ ቤት የመሄድ ልምዴን እንኳን ትቀናቀነኝ ጀመር፡፡ ያቺ ጽጌ የተባለችው ፍጡርማ ጭራሹኑ ከውይይታችን ውስጥ መነሳቷ ቆመ፡፡ ከኔ ጋር የምታሳልፈው ጊዜ በጨመረ ቁጥር ከጓደኛዋ ጋ የምትገናኝበት እየቀነሰ መጣ፡፡
“ዛሬ አርብ አይደል? አልችልም!” እላት ጀመር፡፡ ቅር ሲላት አቤት ደስ ሲል፡፡
አንድ ቀን “እኔም ሲኒማ መግባት እፈልጋለሁ” አለች፡፡
“እሺ፣” አልኳት፡፡
በጨለማው ውስጥ እንደ ንጹህ ውሃ ጠረን - አልባ የሆነ አንገቷ ስር ተሸጉጫለሁ፡፡
“አንተ ክፉ ..” ትለኛለች፡፡
ከንፈሮቿን በከንፈሮቼ ዳበስኳቸው፡፡
ከንፈሮቿ ከሌሎች ሴቶች ከንፈር ጋር አንዳችም ተዛምዶ አልነበራቸውም - ከማር እንጀራ ጋር እንጂ።
ትንፋሽ እስኪያጥራት ድረስ ነበር የምስማት፡፡ አሁንም “አንተ … ተንኮለኛ…” ማለቷን አላቆመችም፡፡ በእርግጥ ብዙ ትንፋሽ አልሰጣትም፡፡ ግን እንደ ምንም በመሳሙ መሃል ጥቂት ፋታ ባገኘች ቁጥር” አንተ ክፉ፣” ትለኛለች
መቸስ - ምን ይደረግ - ታዲያ፡፡
(“የትሮይኑ ፈረስ እና ሉሎች አጫጭር ታሪኮች” ከሚለው መድበል የተወሰደ)    

Published in ልብ-ወለድ
Page 7 of 13