በአንድ እጇ አሜሪካ ውስጥ በሌላው እጇ አፍሪካ ውስጥ ስኬታማ ሥራ ፈጣሪ የቢዝነስ ባለሙያ የሆነችው ሶፊያ በቀለ እሸቴ፣ ወንዶች በገነኑበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በኩባንያ አስተዳደር፣ እንዲሁም በስጋት አያያዝና አወጋገድ ዙሪያ አንቱ የተሰኘች ባለሙያ ነች። በመረጃ (በኢንፎርሜሽን) ደህንነት፣ ጥበቃና ምርመራ ዙሪያ በአለማቀፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች ውስጥ ለበርካታ አመታት የሰራችው ሶፊያ፤ እጇን ወደ አፍሪካ በመዘርጋት እንደ አገር ግንባታ ሊቆጠሩ የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን አከናውናለች። ለአፍሪካ ህብረት እና ለኢትዮጵያ ፓርላማ የተቀናጀ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ስርዓቶችን ዘርግታለች።
ከዚያም የኢንተርኔት ግንኙነትን ከአደጋ ለመጠበቅ በሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎችና እርምጃዎች ዙሪያ የኩባንያ አስተዳደርና የስጋት አያያዝ አማካሪ ሆና ሰርታለች። የኩባንያ ግንባታና የኮሙኒኬሽን አማካሪ በመሆን የአሜሪካ ኩባንያዎችን ከማገልገሏ በተጨማሪ፣ በአለማቀፍ ደረጃም የኢንተርኔት ፖሊሲ አማካሪ ሆናለች። በቅርቡ ደግሞ፣ ዶትኮኔክት አፍሪካ ትረስት (ባለአደራ) እንዲሁም ዶትኮኔክትአፍሪካ ረጂስትሪ ሰርቪስስ ሊሚትድ የተሰኙ ተቋማትን መስርታለች። በዚህም በመላው አለም የሚኖሩ አፍሪካዊያንን በመወከል .africa የተሰኘ የኢንተርኔት አድራሻ ስርወ-ስያሜ ለመፍጠርና በበላይነት ለማስተዳደር ጥያቄ አቅርባለች።  በሰኔ 2004 ዓ.ም ማመልከቻ ያስገባችው፤ አሜሪካ ለሚገኘውና የኢንተርኔት አድራሻዎችን ለሚያስተዳድረው አትራፊ ያልሆነ አለማቀፍ ድርጅት ICANN ነው። ድርጅቱ ውስጥ በምክር ቤት አባልነት ትሰራ በነበረበት ወቅት ነው የዶትአፍሪካ ፕሮጀክቷን የጀመረችው። ዶትኮኔክትአፍሪካ የተሰኙ ተቋሞቿ፤ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም። ተቋሞቿ Yes2dotAfrica  በሚል መሪ ቃል ለስድስት አመታት ያካሄዱት አለማቀፍ የግንዛቤ ማስፋፊያ ዘመቻ ተቀባይነትን አስገኝቶላቸዋል። ዘመቻው፤ በአፍሪካ ስም የኢንተርኔት አድራሻ የመፍጠር ጉዳይ ብቻ አይደለም። በመላው አለም የአፍሪካን መልካም ገፅታ ለመገንባት ልዩ እድል ይሰጣል። በዚያ ላይ፤ የአፍሪካ ሴቶችንና ወጣቶችን፣ በኢንተርኔት አብዮት ውስጥ በዋና ተዋናይነት የሚያሳትፉ በርካታ ፕሮጀክቶችንና እቅዶችን ለማፍለቅ ጥሩ መነሻ ይሆናል።
በአዲስ አበባ የተወለደችው ሶፊያ፣ በወላጆቿ የተደላደለ ኑሮና በጥሩ ትምህርት ነው ያደገችው። ኢትዮጵያ ውስት በተለያዩ የቢዝነስ መስኮች ስኬታማ በመሆን የሚታወቁት አባቷ አቶ በቀለ እሸቴ፤ የህብረት ባንክ እና የህብረት ኢንሹራንስ መስራችና የቦርድ አባል ነበሩ። በአገሪቱ በትልቅነታቸው ከሚታወቁ የገንዘብ ተቋማት መካከልት ህብረት ባንክና ኢንሹራንስ ተጠቃሽ ናቸው። ሶፊያ ከቢዝነሱ ዓለም ጋር የተዋወቀችው፣ ከአባቷ አፍ ነው። ስለ ራሳቸው ስራ ከጓደኞችና ከቤተሰብ አባላት ጋር ሲያወሩ እየሰማች፣ የቢዝነስን አሰራር ትምህርት ቀስማለች። ራስን ችሎ የመወሰንና የመኖር ጥቅምን ከአባቷ የተማረችው ሶፊያ፤ ከስጋት የፀዳ የቢዝነስ ሥራ እንደሌለና ከበርካታ ስጋት አዘል የቢዝነስ አማራጮች መካከል የተሻለውን መርጦ የመግባት ድፍረት አስፈላጊ እንደሆነም መሰረታዊ እውቀት አስጨብጠዋታል።
እናቷ ሲስተር ሙሉዓለም በየነ፣ በሙያቸው ለበርካታ ዓመታት የሰሩ ነርስ ሲሆኑ፣ የማምለክ ያህል በፍቅር ታከብራቸዋለች። ርህራሄንና ደግነትን የተላበሱ በጣም ሃይማኖተኛ ሴት ነበሩ።  በተደላደለ ኑሮ ውስጥ ምንም ሳይጎድልባት ያደገችው ሶፊያ፤ ጥራት ያለው ትምህርት በማግኘትም እድለኛ ነች። ከታላቅ እህቷ ጋር የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው በአዲስ አበባ ናዝሬት ስኩል ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች፣ ከታላቅ እህቷ ጋር አሜሪካ ሄደው ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ ስፖንሰር ስለተገኘላቸው፤ ወደ ሳን ፍራንሲስኮ ካሊፎርኒያ በረረች። በእርግጥ የዩኒቨርሲቲ ወጪያቸውን የሸፈኑት ወላጆቻቸው ናቸው። ከአሜሪካ ኑሮ ጋር መላመድ ለእህትማማቾቹ ፈተና እንደነበር ሶፊያ ስታስታውስ፤ ከተማ ውስጥ ወዲህ ወዲያ ለማለት እንኳ እንደተቸገሩ ትናገራለች። ወቅት የሚከተል የአሜሪካ ዘመነኛ ባህልን በቅጡ ለመገንዘብና መውጪያ መግቢያውን ለማወቅ ጊዜ የፈጀባቸው ሶፊያና እህቷ፤ የራሳቸውን ባህል እንደያዙ የአሜሪካዊያን ሕይወት ውስጥ መቀላቀል ቀላል አልሆነላቸውም። ደግነቱ፤  ጥራት ባለው የናዝሬት ስኩል ትምህርት የታነፁት እህትማማቾች፣ በሳን ፍራንሲስኮ ስቴት ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከሌሎች ተማሪዎች ልቀው ለመገኘት አልተቸገሩም። ለነገሩማ ለተወሰነ ጊዜ ቢደነጋገርባቸውም ከአሜሪካ ኑሮ ጋር መቀላቀላቸው አልቀረም። ከጊዜ በኋላማ ሶፊያ የአሜሪካን ሕይወት መውደድ ጀመረች። ለካ አሜሪካ ልዩ ፀጋ አላት። የአገሪቱ የነፃነት መንፈስ ግሩም ነው፤ ሕይወትን ለማሻሻልና ለመሥራት  ሰፊ እድል የሚገኝባት አገር መሆኗም ድንቅ ነው። ባየችውና ባስተዋለችው መልካም ህይወት ለአሜሪካ ፍቅር ያደረባት ሶፊያ፤ ወደፊትም ያንን አገር ሳትለቅ ነው አፍሪካ ውስጥ እግሯን መትከል የምትሻው። በቢዝነስ አናሊሲስና በመረጃ ሥርዓት (በኢንፎርሜሽን ሲስተምስ) የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከያዘች በኋላ፤ በጎልደን ጌት ዩኒቨርስቲ በማኔጅመንት የመረጃ ሥርዓት ማስተርስ ዲግሪ አግኝታለች። ሥራ ፍለጋ ላይ ታች አላለችም። ሥራው ራሱ ነው እሷን ፍለጋ ዩኒቨርሲቲው ድረስ የመጣላት። በዩኒቨርስቲ እጅግ የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተመራቂዎች፣ ከዩኒቨርሲቲው ሳይወጡ ነው በተለያዩ ምርጥ ኩባንያዎች ተመልምለው ሥራ የሚቀጠሩት። ሶፊያም በወቅቱ በግዙፍነታቸው ከሚታወቁ ባንኮች መካከል አንዱ በሆነው ባንክ ኦፍ አሜሪካ ለኮምፒዩተር ኦዲቲንግ ሥራ ተቀጠረች። በእርግጥ በቀጥታ ሥራ አልጀመረችም። የመረጃ ሥርዓት ደህንነትና ቅልጥፍና፣ በተለይ ደግሞ የመረጃ አጠቃቀምና ጥበቃ ላይ ያተኮረው የኮምፒዩተር ኦዲቲንግ ሥራ፣ ልዩ እውቀት የሚያስፈልገው በጣም አዲስ የሙያ መስክ ስለነበረ፤ ሶፊያና አብረዋት የተቀጠሩ ባልደረቦቿ ባንክ አሜሪካ ውስጥ ተጨማሪ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። እዚህ ወንዶች የገነኑበት ሙያ ውስጥ ነው፤ ሶፊያ ስለ ወንዶች ብዙ ማወቅ የጀመረችው። ወንዶች በበዙበት ድባብ ውስጥ እንዴት ስኬታማና ውጤታማ መሆን እንደምትችል ትምህርት የቀሰመችውም፤ በዚሁ ሥራዋ ነው። ዩኒየንባንካል ወደ ተሰኘው ኮርፖሬሽን ከተሻገረች በኋላ፣ ወደ ሥራ አስኪያጅ የሃላፊነት ደረጃ እድገት አግኝታ ሠርታለች። ከዚያም በአለም በትልቅነታቸው ከሚታወቁ የአካውንቲንግ አገልግሎትና የኢንቨስትመንት አማካሪ ድርጅቶች መካከል አንዱ በሆነው ኩባንያ ተቀጠረች - በፕራይስ ወተርሃውስ ኩፐርስ። ኢንሹራንስና ባንክ የመሳሰሉ ድርጅቶች ገንዘብ ወይም የዋስትና ሰነድ ታቅፈው አይቀመጡም፤ በትርፋማ ነገር ላይ ሊያውሉት ይሞክራሉ እንጂ። ግን ደግሞ፤ ገንዘብ ሲፈልጉ ወዲያውኑ መልሰው ሊያገኙት ይገባል። መፍትሄው፤ ከበርካታ ኩባንያዎችና ተቋማት አክሲዮን ወይም ቦንድ መግዛት ነው። ገንዘባቸውን ትርፋማ ያደርግላቸዋል፤ በአፋጣኝ ገንዘብ ካስፈለጋቸውም የገዙትን አክስዮንና ቦንድ መሸጥ ይችላሉ። እንዲህ በአክስዮንና  በቦንድ ግብይት ገንዘብን ውጤታማ የማድረግ አሰራር፣ ፓርትፎሊዮ ኢንቨስትመንት ይሉታል። ነገር ግን እጅግ አዋቂነትንና ብልህነትን ስለሚጠይቅ፤ በባለሙያ አማካሪዎች አማካኝነት መመራት ይኖርበታል። ፕራይስ ወተርሃውስ ኩፐርስ በተሰኘው ኩባንያ ውስጥ የሶፊያ ዋና ሥራም፣ ለተለያዩ ደንበኞች የፖርትፎሊዮ ኢንቨስትመንት አማካሪ ሆና በበላይነት መቆጣጠር ነበር። የሶፊያን ምክር ከሚቀበሉ ደንበኞች መካከልም በእንግሊዝ ከአራቱ ትልልቅ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው በርክለይ ባንክ ይገኝበታል። ከጤና አገልግሎት ኢንሹራንስ ጋር ለተያያዙና ለሌሎች ኩባንያዎችም የአማካሪነትን ስራ በበላይነት መርታለች። እዚህ ነው ሥራ መምራትን የተካነችው። በአይነትና በመጠን ከሚለያዩ በርካታ ባለሙያዎችና ቡድኖች ጋር የመስራት ችሎታዋ፣ ውስብስብና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የመምራት ጥበቧና ብቃቷ ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋገረ። ይሄኔ ነው የራሷን ድርጅት ለመክፈት የሚያስችል ክህሎትና በራስ የመተማመን መንፈስ መጎናፀፏን እርግጠኛ የሆነችው።
ኩባንያውን ከለቀቀች በኋላ፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ስትዟዟር አንድ አመት አሳለፈች። የሥራ ፈት ዙረት አይደለም። ከአሜሪካ አውሮፓ፣ ከኤስያ ላቲን አሜሪካ ድረስ ወደ ተለያዩ አገራት የተጓዘችው፣ በየአገሩ ያለውን የቢዝነስ አሰራርና ባህል እንዲሁም፤ የኢንተርኔትና የቴክኖሎጂ ደረጃ ለመመልከት ነው። አሜሪካ ውስጥ ሆና በየአህጉሩ ገና በመመንደግ ላይ ለሚገኙ አገራት የቴክኖሎጂ ሽግግር የማካሄድ አላማና የቢዝነስ ውጥን የያዘችው ሶፊያ፣  በ1990 ዓ.ም ሲቢኤስ ኢንተርናሽናል በሚል ስያሜ የራሷን ኩባንያ መሰረተች። በተመሳሳይ አላማም ኢትዮጵያ ውስጥ በ”ሲስተም ኢንተግሬሽን” ሥራዎች ላይ ያተኮረ “ኤስቢኮሙኒኬሽንስ ኔትዎርክ” የተሰኘ ኩባንያ አቋቋመች። ለአፍሪካ ህብረት የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት በጨረታ ተወዳድራ ያሸነፈችው ሶፊያ፣ ለጨረታው የመረጠችው የቢዝነስ ዘዴ፣ በኢትዮጵያ ያን ያህልም የተለመደ አልነበረም። የፕሮጀክት አመራር ላይ በተመሰረተ የቢዝነስ ዘዴ ከአገር ውስጥና ከውጭ ባለሙያዎችንና የተለያዩ ድርጅቶችን አሰባስባ በማስተባበር ጨረታውን ካሸነፈች በኋላ፤ ስራውንም በተመሳሳይ መንገድ አጠናቅቃ ለአገልግሎት አብቅታለች። ገና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባላደገበት አገር፣ በግዙፍነቱ ተጠቃሽ የሆነ የአፍሪካ ህብረት ፕሮጀክት ላይ ውጤታማነቷን ያስመሰከረችው ሶፊያ፤ ወደ ሌላ ትልቅ ፕሮጀክት አመራች። ለኢትዮጵያ ፓርላማ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ስርዓት ለመዘርጋት፤ እንደገና ዳይሜንሽን ዳታ የተባለ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የተውጣጣ ቡድን በመፍጠር ጨረታ አሸንፋ ፕሮጀክቱን በስኬት ፈፅማለች። ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ውዝግብ የተነሳ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰፊ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ የውዝግቡ መነሻ አድሎአዊ አሰራርን በመቃወም ሶፊያ ያቀረበችው ጥያቄ ነው። የግዢና የኮንትራት ሥርዓቱ ላይ ፍትሃዊነት የጎደለው አሰራር መኖሩን በመቃወም ተከራክራ ለማሸነፍ የበቃችው ሶፊያ፤ የመንግስት የግዢና የኮንትራት አሰራር እንዲሻሻል፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትንም እንዲላበስ ክርክሯ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ታምናለች። በ1994 ዓ.ም በግሉ ዘርፍ የተቋቋመ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ የአክሲዮን ገበያ ለመመስረት በማቀድ ለመንግስት ያቀረበው ሃሳብ ስህተቶችና ጉድለቶች እንደነበሩት የምትገልፀው ሶፊያ፣ በመርህ ላይ የተመሰረተ ተቃውሞ እንዳስተጋባች ታስታውሳለች። በዚያው አመት መጨረሻ ላይም ለአክሲዮን ገበያ የቀረበው ሃሳብ በመንግስት ውድቅ ተደርጓል። ምናልባትም በወቅቱ ባስተጋባችው አቋም፣ የኋላ ኋላ የኢትዮጵያ እህል ገበያ እንዲመሰረት መንገዱን የሚጠርግ ነበር ብላ ታስባለች። ኢትዮጵያ ውስጥ አዘውትራ የሰራችበት ያንን ጊዜ ትወደዋለች። ከዘመድ አዝማድም ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ አስችሏት ነበር። በእርግጥ እያሰለሰች ወደ አሜሪካ መመላለሷ አልቀረም። ኩባንያ ወደሚገኝበት ወደ ካሊፎርኒያ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ቁሳቁስ አቅራቢዎቿ ወደሚገኙበት ሚያሚ በተደጋጋሚ ተመላልሳለች። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለአገሯ ተጨባጭ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ፕሮጀክት ያከናወነችበት ወቅት ስለሆነ ግን ያንን ጊዜ ትወደዋለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ የጀመረችውን የፓርላማ ፕሮጀክት እንዳጠናቀቀች፣ ብዙም ሳይቆይ አሜሪካ ውስጥ ሌላ የቢዝነስ እድል ታያት። በአሜሪካ በግዙፍነቱ 7ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ኢንሮን ኩባንያ እንዲሁም በቴሌኮሙኒኬሽንና በኢንተርኔት ቢዝነስ በትልቅነቱ የሚታወቀው ዎርልድኮም ኩባንያ በኪሳራ መዘፈቃቸው በድንገት ይፋ የወጣበትና የዓለም መነጋገሪያ የሆኑበት ወቅት ነበር - ጊዜው።  በእርግጥ ኩባንያዎቹ በድንገት አልከሰሩም። ቅጥ ባጣ የኩባንያ አመራርና በአሳሳች የመረጃ አቀራረብ ለበርካታ አመታት ኪሳራቸው እንዲደበቅ ተደርጓል። የተደበቁት ጉዶች ሲያብጡ ከርመው ድንገት ሲፈነዱ፤ በቢዝነስ ዓለም ከታዩት ትልልቅ ቅሌቶች ተርታ የሚመደቡ ሆነው አረፉት። ታዲያ ለእንዲህ አይነት የመረጃ አጠቃቀምና የኩባንያ አመራር ችግሮች መፍትሄያቸው ምንድነው? ችግሮች ሲኖሩ፣ መፍትሄ ይዞ የሚመጣ ሰው የቢዝነስ እድል ያገኛል።  ሶፊያም በዚህ ምክንያት ነው የቢዝነስ እድል የታያት። የመረጃ ስርዓት ቅልጥፍናንና አጠቃቀምን የመመርመር ሙያዋ ይታወቃል። በትልልቅ ኩባንያዎች ውስጥ በሥራ አመራር የሃላፊነት ደረጃ ሠርታለች። የኩባንያ ንብረቶችን በአግባቡ ለማስተዳደርና ለመምራት፤ የመረጃ ሥርዓት የቱን ያህል ቁልፍ እንደሆነ ታውቃለች። በዚህ ዙሪያ በአማካሪነት ለመስራት በከፈተችው የቢዝነስ ሥራ፣ ካሊፎርኒያ ውስጥ ለሚገኙ በርካታ የሲልከን ቫሊ ኩባንያዎች የምክር አገልግሎት ሰጥታለች - ለኢንተል፣ ጀኔነቴክ፣ ኦንስክሪን ወዘተ።  ለአገሪቱ ብሄራዊ ባንክ (ፌደራል ሪዘርቭ ባንክ) እንዲሁም ለሌሎች ተቋማትም አገልግሎቷን በማስፋፋት ስኬታማ ቢዝነስ ገንብታለች። በኩባንያ ግንባታና በኮሙኒኬሽን እቅዶች ላይም ለበርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎች በአማካሪነት የሰራችው ሶፊያ፣ የሥራ ፈጠራ ኢንቨስትመንት (ቬንቸር ካፒታል)፣ የኮንትራት ሃላፊነትና አፈፃፀም፣ የገበያ እድል ማመቻቸትና ማስፋት፣ የገበያ ድርድር፣ የቢዝነስ እቅድ አመዛዘንና አፈታተሽ፣ የዓለማቀፍ  ትስስር ስትራቴጂያዊ እቅድ አዘገዳጃጀት፣ የሕዝብ ግንኙነት ስትራቴጂ አዘገጃጀትና አፈፃፀም፣ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ የአማካሪነት አገልግሎት አስፋፍታለች።
አዲሱ የአማካሪነት ቢዝነሷን እያስፋፋች ሳለ ነው ተጨማሪ የሥራ አቅጣጫ የሚፈጥርላት አጋጣሚ የተፈጠረው። የኢንተርኔት አድራሻዎችን በሃላፊነት ለማስተዳደር፣ በዓለማቀፍ ደረጃ በመንግስታዊና በግል ዘርፍ ተቋማት ትብብር የተመሰረተው ድርጅት (ICANN)  ውስጥ የምክር ቤት አባል እንድትሆን ተመረጠች። ምክር ቤቱ አንዱ ትኩረት የኢንተርኔት አድራሻ ስርወ-ስያሜ ነው። ለምሳሌ .com, .edu, .gov, .net, .org... የመሳሰሉ አዳዲስ ስርወ-ስያሜዎች ስራ ላይ የሚውሉት በምክር ቤቱ ከታዩና ውይይት ከተካሄደባቸው በኋላ ነው። በስርወ ስያሜዎች አጠቃቀም ላይ በአማካሪነት እንድትሰራ ሃላፊነት የተሰጣት ሶፊያ፣ የኢንተርኔት አድራሻ አሰያየም ላይ መላው የዓለም ማህበረሰብ የመሳተፍ እድል እንዲያገኝ የሚያግዝ የፖሊሲ መመሪያ በማርቀቅ አቅርባለች። ላበረከተችው አስተዋፅኦም በዓለማቀፍ ደረጃ እውቅና ተሰጥቷታል - Internationalized Domain Resolution Union (IDRU) በተሰኘ ቡድን። ሶፊያ የኢንተርኔት አድራሻዎች ላይ በአማካሪነት በምትሰራበት ወቅት ነው፣ ለአፍሪካ ልዩ ትርጉም የያዘ ሃሳብ የመጣላት። .africa የተሰኘ የኢንተርኔት አድራሻ ስርወ-ስያሜ መፍጠርና ሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል በመገንዘብም፣  በ1998 ዓ.ም ዶትኮኔክትአፍሪካ የተሰኘ እቅዷን ማስተዋወቅ ጀመረች። እቅዷም፣ በተለይም በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ፈጣን ድጋፍ አግኝቷል። የመሪነቱን ሃላፊነት በመውሰድ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ባለሙያዎችን አሰባስባ ማመልከቻ በማዘጋጀት፣ በ2004 ዓ.ም ጥያቄዋን ICANN አስገብታለች። .africa የሚል የኢንተርኔት ስርወ-ሥያሜ ሥራ ላይ እንዲውል የቀረበው ማመልከቻ ላይ  በ2005 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል። ሶፊያና ባልደረቦቿ አወንታዊ ምላሽ ያግኙ እንጂ፣ የአፍሪካን መልካም ገፅታ በሚገነባ መንገድ ስርወ-ሥያሜውን ለማስጀመር ዝግጁ ነች። ከዚህም ጋር በማያያዝ፤ የአፍሪካ ሴቶችና ወጣቶች በቴክኖሎጂ መስክ ብቃትና አቅም የሚያዳብሩበት፣ እንዲሁም ቢዝነሳቸውን በቴክኖሎጂ የሚያጎለብቱበት ብዙ አይነት እቅዶችን ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል እያለች በጉጉት ታስባለች። የተራቀቀ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ጨምሮ ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን የመሰለ ሃያል መሳሪያ ወደ ታዳጊ አገራት ለማሸጋገር ባከናወነችው ሥራ ላይ ገለፃ እንድትሰጥ በተደጋጋሚ እየተጋበዘች ተመክሮዋን በተለያዩ መድረኮች አካፍላለች። በኒውዮርክ በተካሄደ የተባበሩት መንግስትት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደ የአፍሪካ መሪዎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስብሰባ፣ እንዲህም በካሊፎርኒያ የስታንፎርድ ሴት የቢዝነስ ባለሙያዎች ስብሰባ ላይ ተሞክሮዋን አቅርባለች።
ሶፊያ ከሙያ ሕይወቷ በተጨማሪ በማህበራዊ አገልግሎቶች ውስጥም ለመሳተፍ ጊዜ አላጣችም። በሮታሪ ክለብ፣ በመረጃ ሥርዓት ኦዲትና ቁጥጥር ማህበር፣ በጎልደን ጌት ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ማህበር የዳሬክተሮች ቦርድ ውስጥ የምትሳተፈው ሶፊያ፣ የሳን ፍራንሲስኮ ቤይ የኢንተርኔት ማህበረሰብን ከመሰረቱት ሰዎች አንዷ ከመሆኗም በላይ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል ናት።
በአብዛኛው ወንዶች በገነኑበት የሙያ ዘርፍ ውስጥ በመስራት ካስተዋለችው ተነስታ ስትናገር፣ ሴቶች ተቀባይነት ለማግኘት በላቀ ብልሃትና ትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል ትላለች። ዋናው ነገር፣ በቁርጠኝነት የሙጢኝ ብሎ መሥራት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሥራዎችሽ እንዲታወቁና እንዲታዩ ማድረግ ያስፈልጋል። ስራዎችሽ ተደብቀው ከቀሩ፣ መልካም ስምንና ዝናን መገንባት አትችይም። የራስሽን ታሪክና የራስሽን ስም ለመገንባት ኢንተርኔትና ማህበራዊ ድረገፆች በእጅጉ ጠቃሚ ናቸው በማለት እሷም እንደምትጠቀምባቸውና እንደምታደንቃቸው ትገልፃለች።
ሶፊያ ለኢትዮጵያ ያላት የወደፊት ተስፋ ብዙ ነው። ከፍተኛ የኢኮኖሚ እምቅ አቅሟን ተጠቅመው እድገትን እውን ሊያደርጉ የሚችሉ፣ በትምህርትና በፈጠራ ችሎታ የበለፀጉ ኢትዮጵያውያን ይታይዋታል። ኢትዮጵያዊያን ጥልቅ ሃይማኖታዊ ትውፊት የታደሉ በመሆናቸው፣  ስርዓትን የሚከተሉና የህግ የበላይነትን የሚያከብሩ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ሰፊ የመናገር ነፃነት እንዲሁም ሰፊ የግል ኢንቨስትመንት ነፃነት እንዲኖራቸው ትመኛለች። በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ አገራቸውን ለመጥቀም የሥራ ፍሬያቸውንና ትምህርታቸውን ይዘው መምጣት ይፈልጋሉ። የኢንቨስትመንት ነፃነት በተሻለ ደረጃ እንዲስፋፋላቸውም ምኞቷ ነው።
ምንጭ፤-
www.ethiopianwomenunleashed..org

Monday, 07 April 2014 15:42

ሃገሬ ትንሳኤሽ

ክፉ ግዜሽ አልቆ
እንባ ከአይንሽ ደርቆ
ሰቀቀንሽ አልፎ
ጥቀርሻሽ ተገፎ
ጉዳትሽ ታክሞ
አጉል ስምሽ ቀርቶ
ብሩህ ፀሐይ ወጥቶ
ማቅሽን አውልቀሽ
ጥበብሽን ለብሰሽ
ጎጆሽን አሙቀሽ
አደይ ተከናንበሽ
ጤናዳም፣ አሪቲ፣ ቄጤማ ጎዝጉዘሽ
በጎችሽ ሳይጎድሉ ሁሉንም ሰብስበሽ
ክብርሽ ተመልሶ
ቃል ኪዳንሽ ደርሶ
ልጆችሽ ተዋደው
ተስማምተው - ተግባብተው
ስትስቂ
ስትስቂ
ስትስቂ የማየው
ሃገሬ ንገሪኝ ዘመኑ መቼ ነው?
ተጻፈ፡- ፯/፯/፳፻፭ ንጋት ፲፪፡ ፭

Published in የግጥም ጥግ

      በአቶ ሥዩም ጣሰው ተጽፎ በአቶ ግርማ ለማ ለህትመት የበቃውን “የንጉሡ ገመና”ን ያነበብኩት በመገረምና በማዘን ሲሆን ይህንኑ ስሜቴን ለኢትዮጵያዊያን በማንፀባረቅ የልጅ ልጅነቴን፣ የውዴታ ግዴታ ለመወጣት በማሰብ በአጭሩ መልስ መስጠትን ወሰንኩ፡፡
በመሠረቱ የአያቴ የቀ.ኃ.ሥ. አልባሽ ነበር የተባለውት ሟች አቶ ስዩም ጣሰው፤ ከበርካታ የንጉሱ አልባሾች መካከል አንዱ እንጂ ብቸኛ አልባሽ ስላልነበር፣ የእሱን ምስክርነት እንደ ወንጌል ቃል ወስዶ አሜን ማለት ኃላፊነት ከሚሰማውና የቀ.ኃ.ሥ(ን) ሥራ ከሚያውቅ ዜጋ የሚጠበቅ ስላልሆነ፣ ህዝብ በመጽሐፉ ላይ የሰፈሩትን በቃለ አጋኖ የተዋቡ መሠረተ ቢስ ወሬዎች ይቀበለዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይልቁንም መጽሐፉን ካለአቅሙ በማግነንና በማጦዝ ለመቸብቸብ የታቀደ መሆኑን በሚገባ የሚያመለክት ክስተት ነው፡፡
የቀ.ኃ.ሥ የግል ኑሮ ከሚወዱትና ይወዳቸው ከነበረው ሕዝብ የተሰወረ አልነበረም፡፡ ስለሆነም ደራሲው በስም ላጲስ ብዕራቸው ያሰፈሯቸው አስነዋሪ ድርጊቶች፣ ከቀ.ኃ.ሥ ማንነት ጋር ግንባር ለግንባር የሚጋጩ እንጂ የሚዋሃዱ አይሆኑም፡፡
ቀ.ኃ.ሥ(ን) አንቆ ገድሎ አልባሌ ቦታ ለ16 ዓመታት ቀብሯቸው የነበረው ደርግና የደርግ ተከታዮች፤ እንደ ከአሁን በፊቱ ዛሬም የቀ.ኃ.ሥ ስምና ሌጋሲን ጥላሸት ለማልበስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ “እውነት ትመነምናለች እንጂ አትጠፋም” እንደሚባለው ዛሬ የቀ.ኃ.ሥ እውነተኛ ማንነት ከትውልድ አገራቸው ባሻገር፣ በዓለም ዙሪያ እየተዘከረ የሚገኝበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
“ዘር ከሐረግ ይጎትታል” ተብሎ እንዳይፈረጅብኝ፣ የኔን መልስ እዚህ ላይ በመግታት፣ ዛሬ በሕይወት ያሉ የቀ.ኃ.ሥ የቅርብ ረዳቶች፣ አልባሾች፣ የቤተ መንግሥቱ ሹማምንቶች መጽሐፉ ላይ ስለሰፈሩት አስጸያፊ “ድርሰቶች” የእውነተኛ ምስክርነታቸውን በመስጠትና ለእውነት በመቆም፣ የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ላበረታታቸው እወዳለሁ፡፡
ቀ.ኃ.ሥ መላ ሕይወታቸውን ለሀገራቸውና ለሚወዱት ህዝባቸው ትርጉም ያለው ሥራ ሰርተው ያለፉ ናቸው፡፡ እንደ ማናቸውም መሪ፤ ታሪክ የራሱ የሆነ ፍርድ ወቅቱን እየጠበቀ ይሰጣል፡፡ ሰዎችን ስም በማጥፋት የሚገኝ ሀብት ግን እንደ ጉም የማይጨበጥ መሆኑን ማወቅ ብልህነት ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ አዲስ አድማስ ጋዜጣ አስተያየቴን ተቀብሎ ለማውጣት በመፍቀዱ የተሰማኝን እርካታ የምገልጸው በታላቅ ምስጋና ነው፡፡

Published in ባህል

አቶ አያሌው  ይመር ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ ዘመን በሦስት መንግሥታት ቤተመንግሥት ውስጥ ሰርተዋል - በኃላፊነት፡፡
በተለይ ጃንሆይ የቤተመንግስቱ ኃላፊ አድርገዋቸው ነበር፡፡ ከንጉሱም ጋር ቅርበት ነበራቸው፡፡
የ84 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው አቶ አያሌው ስለ ቤተመንግሥት ሥራቸውና ስለንጉሱ ከጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ጋር በስፋት አውግተዋል፡፡ እነሆ፡-

ከአፄ ኃይለስላሴ ጀምሮ፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ቤተመንግስት ውስጥ ነበሩ፡፡ እንዴት ነው ቤተመንግስት የገቡት?
በ1952 ዓ.ም ነው  ቤተመንግስት የገባሁኝ፡፡ ጄነራል አበበ ነበሩ ያሳደጉኝ፡፡ አክስቴ 40 ሺ  ሄክታር ቦታ ነበራት፡፡ እዚሁ አሁን ስድስት ኪሎ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ፡፡ አሁንም የምኖረው እዚሁ አካባቢ ነው፡፡ በጣም ሰፊ ነበር፡፡ እኛ የእቴጌ ጣይቱ ወገኖች ነን፡፡ ጎንደር፣ ጎጃም፣ የጁ… የእኛ ነው፡፡ ጠዋት ማታ ጄነራል አበበን ነበር የማስታምመው፡፡ ጄነራል አበበ የታመሙት ቲቢ ነበር፤ ሳንባ በሽታ፡፡ ጃንሆይ መጥተው ሲያይዋቸው ሁልጊዜ ሰላምታ እሰጣቸው ነበር፡፡ “እንዴት ዋልክ” ይላሉ። ሲወጡ ጥጥ በአልኮል ነክሬ በር ላይ እጠብቃቸዋለሁ፡፡ እጃቸውን አልኮል በነካው ጥጥ ጠረግ ጠረግ ያደርጉትና ፈገግ ብለው ያዩኛል፡፡ ጄነራልም ከህመማቸው አላገገሙ እሳቸውን ቀብሬ አክስቴን ልጠይቅ ወደ ስድስት ኪሎ እያመራሁ እያለ… ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሆስፒታል የሚባለው ጋ… አሁን የካቲት 12 ነው መሰለኝ የምትሉት “ጃንሆይ መጡ መጡ” ተባለ፡፡ እንዳጋጣሚ ነው አየት አድርገው ያወቁኝ፡፡ እናም አስጠሩኝ፡፡
“የት ነው ያለኸው?” አሉኝ፡፡
“አክስቴ ጋ” አልኳቸው፡፡ አንገታቸውን ወዝወዝ አድርገው አለፉ፡፡
ቤት ሄጄ የተባልኩትን የሆነውን ሁሉ ለአክስቴ ነገርኳት፡፡ አክስቴም “ምን ይታወቃል… ሊያሰሩህ ይሆናል” አሉኝ፡፡ አንድ ጠዋት የእቴጌ ዣንጥላ ያዥ (ረጅም ነው) ተልኮ ቤታችን መጣ፡፡ “ኧረ ተካ ገዳ… ከመቼ ወዲህ…” አሉ አክስቴ፡፡
“የድሮው ጠጅ የለም እንዴ… እሜቴ?” እያለ እያጨዋወታቸው ወደ ቤት ዘለቀ፡፡
“የጄነራል አበበ አሽከር የነበረውን አምጣ ተብዬ ነው” አላቸው፡፡ ከቤት ይዞኝ ሄደ፡፡ ስድስት ኪሎ ልደታ አዳራሽ በፊት ለፊት በር ይዞኝ ገባ፡፡ ጃንሆይ እጄን ይዘውኝ፤
“ከዛሬ ጀምሮ ከዚህ እንዳትነቃነቅ” አሉኝ፡፡ በቃ! እዚያው ቀረሁ  ቀረሁ፡፡
ቤተመንግስት ውስጥ ምን ነበር የሚሰሩት?
በፊት የመጠጥ ቤት ኃላፊ ነበርኩ፡፡ በኋላ ከመጠጡ ወጥቼ ምክትል የእልፍኝ አስከልካይ ሆንኩ፡፡ ሴት ወይዘሮና መኳንንቱን ከእቴጋ ጋር አገናኝ ነበር፡፡ እቴጌ ቢሮ ነው የሚቀመጡት፡፡ የተበደለውን፣ ፍርድ ጐደለብኝ የሚለውን “ውሰድና ለእገሌ አገጣጥም፣ በቶሎ ፍርዱ ይታይለት” ብለው ያዙኛል፡፡ ጃንሆይም ለብቻቸው ችሎት አላቸው፤ በችሎታቸው ያስችላሉ፡፡ ምሳ ሲደርስ መኳንንቱ ይመጣሉ፤ ጃንሆይ ጋ ምሳ ለመብላት፡፡ ጃንሆይ ያን ምሳ ይጋብዙና ወደ ማረፊያቸው ይገባሉ፡፡ ጠዋት ፆም ከሆነ፣ ፀሎታቸውን ጨርሰው ለባብሰው ነው ቁጭ የሚሉት። ስድስት ሰዓት ሲሆን የህዝብ ችሎት ቀርበው ያሟግታሉ፡፡ ከዛ ቅዳሴ ካለ ተነስተው ይሄዳሉ፡፡  
ቀጠሮ ሲኖር ማስታወሻ እንይዛለን፡፡ “በዚህ ሰዓት እንግዳ ይመጣል” ብለን ለጃንሆይ እንነግራለን፡፡ አስተርጓሚው ይገባሉ፤ እኛ እንወጣለን። እኔ ለእቴጌም ለጃንሆይም ቅርብ ነበርኩ፡፡  መንግስቱ ንዋይ ያንን ካደረገ በኋላ እኮ (መፈንቅለ መንግሥቱን ማለታቸው ነው) የታችኛው ቤተመንግስት የቢሮዋቸው ኃላፊ አድርገውኝ ነበር፡፡ አዛዡ፣ ሊጋባው፣ አጋፋሪው… ብዙ ብዙ ደረጃ ነበር፡፡ ጠቅላዩ ግን የቤተመንግስቱ ሚኒስትር ናቸው፡፡ በእኔ ሥር አስራ አምስት ሰራተኞች ነበሩ፡፡ ጃንሆይ ብሔራዊ ቤተመንግስት ነው የሚበሉትም የሚያድሩትም፡፡ ፈረንጆች አንዳንድ ገፀ በረከቶች ሲሰጡዋቸው፤ ያንን አንስቼ አስቀምጣለሁ፡፡ በኋላ ያዩትና… “ምንም የሚረባ ነገር አይደለም… ብቻ ይሁን” ይላሉ፡፡
እስቲ የጃንሆይን የዕለት ዕለት ተግባር ይንገሩኝ...?
ከጠዋቱ በ12 ሰዓት ላይ ወታደሩ ከአንደኛ በር ተነስቶ፤ በሰልፍ ሂዶ ነው ባንዲራ በጥሩንባ የሚሰቅለው፡፡ የባንዲራ መስቀያው ፊት ለፊት የእሳቸው መኝታ ቤት ነው፡፡ በራቸውን ወለል አድርገው አንደኛ በር ድረስ ያያሉ፡፡ የጠዋት የሙቀት ልብሳቸውን ለብሰው፤ በዛውም ወደ ፀሎት ይሄዳሉ፡፡ የፀሎት ስፍራቸው፣ ከእንጦጦ ማርያም ትይዩ ነው፡፡
ወደ ፀሎት ሲያዘግሙ “እንዴት አደራች” የለም፤ ዝም ነው የሚሉ። ሰው አያነጋግሩም፡፡ ፀሎታቸውን ሲያበቁ ነው የሚያነጋግሩት፡፡ ከላም አላቢዎችና ፈረስ ቦራሾች በቀር በዚያች አካባቢ ዝር የሚል የለም፡፡ ዳዊቱን የሚደግሙት በቃላቸው ነው …ግዕዙን እኮ ነው፡፡ በ12 ሰዓት ጠዋት የቆሙ ሁለት ሰዓት ሲሆን የቆሙባትን መሬቷን ሳም አድርገው ነው የሚነሱት። ከዛ የከብቶቹን ኃላፊ ይጠሩታል፡፡
“ተሰማ … ላሟ ጥጃዋን ስትዋጋት አላየህም … ለምንድነው?” ይላሉ፡፡ ወደ ፈረሶቹ ዘወር ይሉና ደግሞ፤ “ክፍ.. ሲነክሰው ዝም ብለህ ታያለህ፤ አላየሁም መሰለህ … ሁለተኛ ተጠንቀቁ” ይላሉ፡፡  
እስቲ ስለ1953 ዓ.ም. የታህሳስ ግርግር፤ ይንገሩኝ…?
እዚያው ቤተ መንግስት ውስጥ ነበርን፡፡ መንግስቱ ንዋይ እኮ ነው፡፡… ጃንሆይ ፈረንጅ አገር ሄደዋል፡፡ እቴጌ… መኳንንቱ ሚኒስትሮቹ አሉ፡፡ እኛ አላወቅንም፡፡ ማታ 4፡30 ወደ 5 ሰዓት ገደማ ነው- እኔ ወደ ቤቴ የምገባው፡፡
ለምን?
ቁልፍ ይዣለኋ!
የምን ቁልፍ?
የመጠጡን ነዋ! እቴጌም ቢኖሩ ያው እንደ ጃንሆይ ናቸው፡፡ ጃንሆይ የትም ለመሄድ ሲያስቡ ድብቅ ነው፡፡ ያኔም ለህዝብ አልተነገረም፡፡ የሚያውቅ ግን ያውቃል፡፡ ከዚያ እንግሊዝ አገር ሆነ መቀመጫቸው፡፡ ቆይተው ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ወሰዱ፡፡ የጃንሆይ አባት ራስ መኮንን፣ እንግሊዝ አገር የሠሩት ቤት አለ - “ፌርፊልድ ቤተመንግስት” ብለዋታል ጃንሆይ፡፡ ከከተማው ወጣ ብሎ ነው የሚገኝ፡፡
እርስዎ የእንግሊዙን ቤተመንግሥት የማየት ዕድል ገጥሞዎታል?
አላየሁትም፡፡ ጃንሆይ ከተመለሱ በኋላ በተራ እንደወስዳችኋለን ብለው ነበር፡፡ እድላችን ሆኖ አልሄድንም፡፡ በፎቶግራፍ ግን አይቼዋለሁ። እና ጃንሆይ እንግሊዝ አባታቸው ቤት ገቡ፤ ልጆቻቸውንም ባለቤታቸውንም ወሰዱ፡፡ ትንሽ የተማሩትን ባለስልጣናትም ወስደዋል፡፡ ሃሳባቸው የጣልያንን ወረራ ለዓለም ከፍተኛው ፍ/ቤት ማቅረብ ነበር፡፡
መንግስቱ ንዋይ መክዳቱን ጃንሆይ አውቀዋል። በስምንተኛው ቀን ቤተመንግስቱ በታንክ ተከቦ… ስራ ልንገባ ስንሄድ አይቻልም አሉለን፡፡ ሚኒስትሮችን ማታ “እቴጌ ታመዋል” ብሎ ጠርቶ አጐራቸው። እቴጌ የራሳቸው ቤት አለ፤ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጐን፤ የእናታቸው ቤት ነው፤ እዛ ገቡ፡፡ ሲነጋ ሄድን፤ ሰውም ዙሪያውን ከበበ፡፡
ወዲያው አልጋ ወራሽ በሬዲዮ “እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሆኜ ለአገሬ ላገለግል በተቆረጠልኝ ደምወዝ…” የሚል ነገር ሲናገሩ ክው አልን፡፡ “አስገድዷቸዋል…” አልነ፡፡
ጠቅል ይህን ሲሰሙ ባሉበት ሆነው ብድግ አሉ።
“ህዝቤን እኔ አውቀዋለሁ፤ ህዝባችን እኛን ይወደናል፤ ግዴለም እኛ ከአንድ ከሁለት ሰው ጉዳይ የለንም” ብለው ገሠገሡ፡፡ አስመራ ሲገቡ የአስመራ ህዝብ “እኛ እንቅደም እርስዎ ይቆዩ” አለ.. “አይ ግዴለም” ብለው መጡ፡፡ ያኔ አውሮፕላን ማረፊያው ጦር ኃይሎች ነበር፡፡ ያን ጊዜ የቦሌው አውሮፕላን ማረፊያ አልተሠራም፡፡ እዚያ ሄደን ንጉሱን ጠበቅናቸው፡፡ መሬቷ አትታይም፡፡ ህዝቡ ለጉድ ነበር፡፡ ጃንሆይ ፈገግ ፈገግ እያሉ ነበር፡፡ አቡነ ባስሊዎስ ከጐናቸው ነበሩ፡ የጦር ሚኒስትሮቻቸው ጀነራል መርድ መንገሻና ጀነራል ከበደ ገብሬ ነበሩ መንግስቱ ንዋይን ድል ያደረጉት፡፡ ሰራዊቱ ተዋጋ፡፡ ለካ ግማሹ ክቡር ዘበኛም አላወቀም፡፡ “እንግሊዝኛ ቆጠርን!!” የሚሉት ናቸው የከዱት። ጃንሆይ ቀጥታ ልዕልት ተናኘ ቤት ነው የገቡት፡፡ ቆዩና ብሔራዊ ቤተመንግስት ገቡ፡፡ ለሊቱን ሙሉ ተኩስ ነበር፡፡ ጃንሆይ  “እባካችሁ ከልክሉ” ይላሉ። አበበ አረጋይም ተው ይላሉ፡፡ ጃንሆይ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሆስፒታል ሄደው ብዙ ሬሳ ተመለከቱ። ሬሳው ሲታይ “እነ ራስ ስዩም፣ እነ አበበ አረጋዊ… ሚኒስትሮች ሁሉ… ነበሩበት፡፡ መንግሥቱ ንዋይ ኩዴታው መክሸፉን ሲያውቅ ቀጨኔ መድሃኒያለም ተደብቆ፣ ሌሊት ወደ ሶማሊ ሲሄድ ዝቋላ ላይ ተያዘ። ተታኮሰ፤ አንድ አይኑን መቱት፡፡ ወንድምየውን ገደሉት፡፡ እሱን ወደ ጃንሆይ አመጡት፡፡ ብርድ ልብስ ለብሶ ባዶ እግሩን ነበር፡፡
“መንግስቱ” አሉት ጃንሆይ፤ አንድ ዓይኑ አያይም “ያ ሻምፓኝ የምትጠጣበት ቤተመንግስት ነው” “አይታየኝም” አላቸው፡፡ ይኸኔ “ውጡ ውጡ” ተባልንና ወጣን፡፡ እሱና እሳቸው ብቻ ቀሩ፡፡ ህክምና ተደረገለትና ለፍርድ ቀረበ፡፡ ያ ሁሉ ደመኛ ዘመድ መጣልሽ፡፡ ከፍተኛ ፍ/ቤት ሰው ግጥም አለ። የሞት ፍርድ ተበየነበት፡፡
ተክለ ሃይማኖት አደባባይ መሰላል መስቀያ ተዘጋጅቶ ለንጋት አጥቢያ ላይ በ12 ሰዓት ህዝቡ ግጥም ብሏል፡፡ መንግስቱ ገበር ጅንስ ሱሪና ከላይ ሸሚዝ ነበር የለበሰው። የመስቀያውን ደረጃ ጢብ ጢብ ብሎ ወጣ፤ ወዲያው መሰላሉን ሸርተት አደረጉት፡፡ በአደባባይ ተሰቀለ፡፡ ከዛ አብረው የኖሩት መርድ መንገሻ ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡
ምክትል እልፍኝ አስከልካይ ሆኜ እሰራ ነበር፤ ለእቴጌ መነን፡፡ ጃንሆይ ወታደሩንም፣ ሹማምንቱንም ሰብስበው “የተወለድኩበትን የአባቴን ቤት ለዩኒቨርስቲ አስረክቤዋለሁ” አሉ፡፡ ያ ሁሉ ሚ/ር የተረሸነው እዛ ውስጥ ነው፡፡ ግብዣቸውን አድርገው ብሔራዊ ፍልውሃ ቤተመንግሥት ገባን። ያን ጊዜ እሳቸው ህዝባቸው እንዲማርላቸው፣ ያን ጊዜ ጨለማ ነው፤ ትምህርት የለም፡፡ በየአገሩ፣ በየወረዳው እየሄዱ እንጨት አጣና እየረበረባችሁ ት/ቤት አቋቁሙ አሉ፡፡ መጽሐፉን ሁሉ በመኪና እየጫኑ እየሄዱ ይሰጡ ነበር፡፡
በቅርቡ የወጣ መጽሐፍ፤ ጃንሆይ ጥፋት የፈፀሙ የቤተመንግሥቱ ባለሟሎችን በአለንጋ ይገርፉ እንደነበረ ይገልፃል፡፡ እርስዎ ይሄን ያውቃሉ?
ጃንሆይ!!? (ራሳቸውን ይዘው እየነቀነቁ) ጠርተው “ተው! እንደዚህ አይነት ብልግናህን ተው!” ብለው ነው የሚመክሩት፡፡ ብለው ብለው ሲያቅታቸው “አለንጋ አምጡ” ብለው…ትንሽ ነካ አድርገው ነው የሚተውት፡፡
ይኼው መጽሐፍ ...ስስት አለባቸው ይላል ንጉሡን?
ውሸት ነው፡፡ በልተሸ የጠገብሽ አይመስላቸውም እኮ፡፡ “አንሺ፣ ብይ… ያወጣሽውን ምግብ መጨረስ አለብሽ” ነው የሚሉሽ፡፡ ሴት ወንድ ሳይሉ ይጋብዛሉ፡፡ እሳቸው የሚቆጡት መብራትና ውሃ ያለጥቅም ሲባክን ነው፡፡ “መብራትና ውሃ ማን አባቱ ነው የሚከፍተው? ጥራ ማን ነው የከፈተው ይሄን ውሃ፤ እናንተ አታውቁትም፤ እኛ እናውቀዋለን የውሃን ጡር” ይላሉ፡፡
የጃንሆይ አመጋገብ እንዴት ነበር?
ጃንሆይ የእኛን ሀገር ምግብ ብዙም አይወዱትም ትንሽ አልጫ ነበር የሚወዱት፡፡ በተረፈ ግን የፈረንጅ ምግብ ነው የሚመርጡት ኬክ ከምግብ በኋላ ሳይሆን በ10 ሰዓት ከሻይ፣ ከወተት ጋር ሆኖ ይቀርብላቸዋል፡፡ ራሳቸው የሚፈልጉትን ያህል ቆርጠው ነው የሚበሉት፡፡
እቴጌ ጣይቱ የአፄ ምኒልክ ቀኝ እጅ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ የአፄ ኃይለሥላሴ እቴኔ መነንስ እንዴት ያሉ ነበሩ?
እቴጌ እንኳን ፀሎተኛ ናቸው፡፡ እቴጌ ጣይቱማ በጦሩም ጭምር አሉበት፡፡ እኝህ እቴጌ መነን ፀሎት ብቻ ነው፤ ደግ ሰው ነበሩ፡፡ በፀሎት ጥሩ አድርገው አገራቸውን የረዱ ሰው ናቸው፡፡ መንህፍት ማንበብ፣ ዳዊት መድገም እንጂ ሌላ የሚያውቁት ነገር የለም። ብቻ ከፈረንጆቹ ጋር ቀጠሮ ሲኖራቸው በአስተርጓሚ መልስ ይሰጣሉ፡፡ ጃንሆይን ያልሽ እንደሆነ ደግሞ የደግነታቸውና የአስተዋይነታቸውን ብዛት አልነግርሽም። መኳንንቱ እንደመሰለው ሲፈርድ… እሳቸው ችሎት ቀርበው ጉዳዩ ሲነበብ ልብ ብለው ያደምጣሉ፡፡ “እዚች ጋ ምልክት አድርግ” እያሉ ተነቦ ሲያልቅ.. “እስቲ ቅድም ምልክት ያደረክበትን አንብብ” ይላሉ መልሰው፡፡ ያ ሁሉ ተደርጐ ነው እሳቸው የሚፈርዱት፡፡ ከዚያ “ርስቱን ቀማኸው፤ አያቱ አድዋ ዘምቶ፣ አባቱም ማይጨው ሞቶ አንተ ጣሊያን ሰጠኝ ብለህ የያዝከው መሬት አይደለም… ለእሱ ይገባል” ብለው ይፈርዳሉ፡፡ ልጃቸው ቢሆንም እንኳ ለሃቅ ነው የሚፈርዱት፡፡ ልብ እንደ ጐራዴ ተመዞ አይታይ እንዴት ብዬ ልንገርሽ? ለፍርድ በጣም ይጠነቀቃሉ፡፡ እንደሳቸው ጥንቁቅ ማንም የለም። ጠዋት ማታ ፖለቲካውን አስተዳደሩን… ይከውናሉ። በቀኛቸው ዶሴ በግራም ዶሴ ነው፡፡ የሞት ፍርድ እሳቸው ካልፈረሙበት አይፈፀምም፡፡ የፍርድ ሚኒስትሩ አቶ አካልወርቅ “ጃንሆይ ያን ነገር እባክዎ አዘገዩት” ይሏቸዋል፡፡
እሳቸውም “ሰው ለመግደል ምን ያስቸኩልሃል?” ይሉታል፡፡ ይሄኔ ዝም ይላል፡፡ ሁልጊዜ የሞት ፍርድ ላይ ፊታቸውን አዙረው ፀልየው ነው፡፡ ምን ያድርጉ… ፍርድ ነዋ፤ አይቀር!
ቀደም ሲል በጠቀስኩልዎት “የንጉሱ ገመና” መፅሃፍ ላይ “ሴሰኛ” መሆናቸውና ከቤተመንግሥት የፅዳት ሠራተኞች ጋር ሳይቀር ይቀብጡ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ይሄስ ምን ያህል ሃቅ ነው?
አይ ሰው ከንቱ! ይሄን አለም የተውት ገና ከስደት ሲመጡ ነው፡፡ ግን እሳቸው ምን ቸገራቸው! አየሽ… ባላደረግሽው ነገር ስትታሚ እግዚአብሔር ነው ዋስሽ። እሳቸውን ማንም የሚጠረጥራቸው የለም። ባይሆን እንኳ እነ ልዑል መኮንን… ልጆች ስለሆኑ ጨዋታ ይፈልጉ ይሆናል፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ የተማሩ እኮ ናቸው፡፡ የሊቁን ትምህርት በግዝ ሲነግሩሽ… ሌላ ነው፡፡ አባታቸው ራስ መኮንን ጥሩ አድርገው አስተምረዋቸዋል፡፡ ኦሮምኛ ሲናገሩ ጥርት አድርገው ነው፡፡ በእርግጥ ንጉስ ስለሆኑ በአስተርጓሚ ነው የሚሠሙት፡፡ አንዴ መንገድ ሲሄዱ አንዱ “ጃንሆይ ተበደልኩ” እያለ በኦሮምኛ ይማፀናል፡፡ ጃንሆይም አብሯቸው ያለውን ሰው “ምን አለ?” ብለው ጠየቁት፡፡ እሱ ለካ ኦሮምኛ አይችልም፡፡
“ኧረ እኔ አላውቀውም ጃንሆይ” አላቸው፡፡
“ምን አባክና የአገርህን ቋንቋ አታውቅም” ብለው ገሰፁት፡፡ እሳቸው ገጠሙታ በኦሮምኛ፡፡ አደርኛም አረብኛም ትግርኛም ይሰማሉ፡፡ ንጉስ ስለሆኑ ግን ሁሉንም በአስተርጓሚ ነው፡፡
ከበደ ተሰማን ያውቋቸዋል?
ደጃች ከበደ ተሰማ አብረን ኑረን አይደል፡፡ ጥንት የዘውዲቱ አሽከር ነበሩ፡፡ በምኒልክም ትንሽ ልጅ ናቸው እንጂ መድረስ ደርሰው ነበር፡፡ ጃንሆይ ከነገሡ በኋላ ደጃዝማች ብለው ጠቅላይ ገዢ አደረጉዋቸው፡፡
በፊት አሽከር ነበሩ፡፡ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ለጃንሆይ ቅርብ ነበሩ፡፡ ዕውቀታቸው የሀገር እንጂ የውጪ ትምህርት አልነበራቸውም፡፡ ብልሃተኛ ነበሩ፡፡ እነ ከበደ ተሰማ እየሩሳሌም ተቀምጠው፣ ጃንሆይ እንግሊዝ እያሉ፣ ምስጢር ይነጋገሩ ነበር። ከበደ ተሰማን ጥሩልኝ ብለው ከእየሩሳሌም በፖርት ሰይድ፣ በግብፅ አድርገው እንግሊዝ አገር ገቡ፡፡ የኢትዮጵያ መሬትን ከረገጡማ ጣሊያን ይይዛቸዋል።
በእንግሊዝ ከተገናኙ በኋላ “እንግዲህ አንተን የጠራንህ በኢትዮጵያ ጦርነት ተነስቷል፤ እየቀደምክ ወረቀት እየፃፍክ ለጎንደር፣ ለጎጃም፣ ለሸዋ፣ ለትግሬ፣ ለኦሮሞ… በምስጢር ላክ፤ “ጃንሆይ መጡ ጃንሆይ መጡ” እያልክ አሏቸው፡፡ ከዚያም ጣሊያን እንዳይማርካቸው ከእንግሊዝ ጦር ጋር እየተከተሉ፤ ለጎንደር ህዝብ በአውሮፕላን ወረቀት ተበተነ። እልልታው ፈነዳ፡፡ ያን ግዜ በቤተመንግስት ባንሆንም የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴን “መጣሁልህ አይዞህ” የሚል ወረቀት ስናነብ ለቅሶ ሆንን፡፡
ከዚያ እሳቸው ጎጃም ገቡ... የአርበኛውን ጦር ለማየት እዛው ቁጭ አሉ፡፡ አርበኛው ሁሉ ገብቶ ገብቶ ሰልፉን አሳይቷል፡፡ “በላይ ዘለቀ ነገ ይመጣል” ተባለ፡፡ ጃንሆይ ከመጓጓታቸው የተነሳ ጠዋት በ4 ሰዓት የተቀመጡ አልተነሱም፡፡ በኋላ ምሳ ሰዓት ሊደርስ ሲል መጣ፤ በፈጥኖ ደራሽ በወጣት ጦር ታጅቦ፡፡ “የገሊላው” አሉ፤ የጃንሆይ ወንድም ራስ ካሣ ከጃንሆይ ጎን ተቀምጠው። ሲደነግጡ የሚጠቀሙበት ዘይቤያቸው ነው፡፡ በላይ ዘለቀ መጥቶ ከጃንሆይ ፊት ቆመ፡፡
“በላይ ዘለቀ ማለት አንተ ነህ? እንደ ጆሮህ ትልቅ፤ እንደ አይንህ ትንሽ” አሉት፤ ጃንሆይ። (ዝናህን ስንሰማ ትልቅ ዕድሜ ያለህ መስሎን ነበር ማለታቸው ነው) ልጅ ነው፤ ፈጣን፡፡ እሱም ከጐናቸው ተቀመጠ፡፡ የልጅ ነገር ሆነና በገዛ እጁ ሞተ፡፡ የጎጃም ጠቅላይ ገዥ እሆናለሁ ብሎ ነበር፤ ውስጥ ውስጡን፡፡ ሰው ክፉ ነው አጣሏቸው፤ እዚህ መጥቶ ታሰረ፡፡ ከእስር ቤት ሰብሮ አመለጠ፡፡ ሱሉልታ ላይ መቶ አለቃውን በጥይት ገደለ፡፡ በመጨረሻ ተያዘና ለፍርድ ቀረበ። …ጃንሆይ እንዲሞትባቸው አልፈለጉም ነበር፡፡ በፍትሃ ነገስቱ… “በግፍ የገደለ ይገደል” ስለሚል ተሰቀለ፤ ጎጃም አኮረፈ፡፡
በላይ ዘለቀን በደንብ ያውቁት ነበር?
የአክስቴን ቤት ተከራይቶ ነበር የሚኖር። ጠይም የሚምር ቆንጆ፣ ጀግና ነበር፡፡ አክስቴ ከምግቡም ከቅቤውም ከማሩም ለበላይ ሰራተኞች ውሰዱ ይሉናል፤ ወስደን እንሰጣለን፡፡ ቤቱ ስንሄድ እንደ ገጠር ቤት በየቦታው በገል ጢስ ይጢያጣሳል። ይኼን ሳይ “ምንድን ነው” ብዬ አክስቴን ጠየኩዋት። “በሽታ እንዳይነካው ይሆናል” ብላ ሸፋፈነችለት… ነገሩ እንኳን ሌላ ነው፡፡ አንድ ሁለት ወር ያህል እንደተቀመጠ ቤት ተሰጠውና ወጣ፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ደሃቸውን የሚወዱ ነበሩ፡፡
ደመወዝዎ ስንት ነበር?
40 ብር ነበር፡፡ በእኛ ግዜ በጣም ብዙ ነበር፤ የትየለሌ ነው፡፡ ባለቤቴ የቤትዋን ጣጣ ትጨርስበታለች ወሩን ሙሉ፡፡ አንዲት ጠቦት በግ ለመግዛት አስራ አምስት ብር እንኳን አይፈጅም ነበር፡፡
በቤተ መንግስት ውስጥ በኃላፊነት ላይ ከነበሩ ሰዎች በተለየ ከነገስታቱና ሹማምቱ ጋር ቁጭ ብለው ፊልም እንዲያዩ ይፈቀድልዎት ነበር ይባላል?
እኔ ቆሜ ነበር የማየው፡፡ ጃንሆይ ካላዘዙ ማንም የሚቀመጥ የለም፡፡ ምግብ የሚያቀርብላቸውን እሸቱን ጠርተው “ከብላታ አድማሱ ጀርባ ለአያሌው ወንበር አስቀምጡና ፊልም ይመልከቱ” ብለው አዘዙ። ራት በልተን ልንወጣ ስንል ተጠራሁና፤ ፊልም ማየት እንደተፈቀደልኝ ነገሩኝ… እጅ ነሳሁና ተቀመጥኩ፡፡
ቤተመንግሥት ምን ዓይነት ፊልሞች ነበር የሚታዩት?
የጀርመን የሁለተኛ የዓለም ጦርነትን ፊልም ነበር የምናየው፡፡ ጃንሆይ ፊልም ሳያዩ አይተኙም፡፡ ስድስት ኪሎም ሆነ ብሔራዊ ቤተመንግስት ረዣዥም ፊልሞችን ይመለከቱ ነበር፡፡ ለእቴጌ የልዕልት ተናኘ ልጅ ሒሩት ከጎናቸው ቁጭ ብላ ታስተረጉማለች፡፡ እቴጌ እንግሊዝኛ አያውቁም፡፡
አፄ ኃይለስላሴ እንግሊዝኛ በደንብ ይችሉ ነበር?
እንዴታ! በደንብ ነዋ! ፈረንሳይኛማ ከልጅነታቸው ጀምረው እንደውሃ የጠጡት ነው፡፡ እንግሊዝኛ ሲናገሩ የዋዛ መሰሉሽ፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ የሚባሉ የእርሳቸው ሀኪም ማታ ማታ ከአጠገባቸው አይጠፉም ነበር። በ11 ሰዓት የመጡ ማታ ፊልም ሲያልቅ ከጃንሆይ ጋር ተነስተው ነው የሚሄዱት፡፡ ጃንሆይ በፈረንሳይኛ የሚያወሩት ታዲያ ከሀኪማቸው ጋር ብቻ ነበር፡፡
እስቲ ከዙፋናቸው የወረዱበትን ሁኔታ ይንገሩኝ…
የያዝዋቸው ቤተመንግስት ውስጥ ነው፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም የመጣው ሐረርጌ ኦጋዴን የጦር ኃላፊ ሻምበል ሆኖ ነው፡፡  ወደዚህ እንደመጣ ዋና አደረጉት። “ሻምበል መንግስቱ” … “ሻምበል መንግስቱ” አሉት። ጃንሆይን የያዟቸው ጊዜ፤ “ሰማችሁ ለውጥ ያለ ነገር ነው፤ በእኛ ብቻ አልተጀመረም፤ ግን የአስመራን በር መከራ አይተን ያመጣነው ነውና ተጠንቀቁ፡፡ ኦጋዴኑን ተውት ግዴለም፤ ይሄንን ግን ተጠንቀቁ፤ አደራ አገሪቱ እንዳትሞት” ብለው ነው አጅሬ የተናገሩት፡፡ ሁላችንም አለቀስን፡፡ አፄ ምኒልክ ቤተመንግስት አመጧቸው፡፡ ደበላ ዲንሳ የሚባለው… ሰዎች ይዞ መጥቶ የተፃፈ ነገር በክብር አነበበላቸው፡፡ ከዚያም ግርማዊነትዎ፤ “ወደ ተዘጋጀልዎ ማረፊያ እንዲሄዱ ፍቀዱልን” አሏቸው። እሺ አሉ፡፡ ከጎናቸው እራስ እምሩ አሉ፡፡ “ይሄ ያለ ነገር ነው፤ ብቻ የአገራችሁን ነገር አደራ… አደራ” አሉ፡፡ ለረጅም ሰዓት ሰው ሁሉ ተላቀሰ፡፡ አታንሺብኝ እባክሽ። ለምን መጣሽብኝ?… አመት አቆይዋቸውና አንድ ቀን “ግርማዊ ንጉሰ ነገስት ባደረባቸው ህመም አርፈዋል” ብለው ተናገሩ፡፡ አለቀስን፡፡ ከንቱ ነው ይሄ አለም እባክሽ፡፡  
በእስር ቤት እያሉ ያገኙዋቸው ነበር?
የእቴጌ ጣይቱ መኝታ ቤትና የአፄ ምኒልክ መኝታ ቤት ግራና ቀኝ ነበር፡፡ ሁለቱም የሚገናኙት በሰገነት ነበር፡፡
የአፄ ምኒልክ ልጅ ዘውዲቱ ነግሰው አልነበር፤ የጃንሆይ አልጋ ወራሽ ሆነው፡፡ ምድር ቤት እራት የሚበሉበት ስፍራ ነበረች፡፡ እዛ ውስጥ ነው መንግስቱ ለአፄ ኃይለስላሴ ማረፊያ እንዲዘጋጅ ያዘዘው። መንግስቱ ኃይለማርያም… “እርስዎ” እያለ ነበር ትእዛዝ እንኳ የሚያዘን፡፡ ከአፉ “አንተ አንቺ” የሚል አይወጣውም ነበር፡፡ ከሶስት ከአራት ቀን በኋላ… አስጠራኝና “የእስረኞች አዛዥ እርስዎ ነዎት?” አለኝ፡፡
የእነዚያ ሁሉ እስረኞቹ ሃላፊ ነኝ፡፡ በአፄ ምኒልክ አዳራሽ ነበር ያ ሁሉ እስረኛ የታሰረው፡፡ እና ወደ እስረኞች ስገባ መናገር የምፈልገውን ነገርኳቸው። “እኔን ግባ ካላችሁኝ … ስገባ “እንደምን አደራችሁ፤ እግዚአብሔር ያውጣችሁ” እላለሁ፤ ስል “ይሄንንስ ማለት አትችልም” አለኝ አንዱ፡፡
“ይኼን ካላልኩ አልገባም” አልኩ፡፡ ተጠራሁና “ይበሉ” ተብዬ ተፈቀደልኝ፡፡ ሚኒስትሮቹ እነፀሃፊ ትዕዛዝ አክሊሉ፣ መኳንቱ ሁሉ በስሜ ነበር የሚጠሩኝ። እስረኞቹ ከእኔ ጋር አብረው የነበሩ ናቸው፤ ብዙ አገለገልኳቸው፡፡
መንግስቱን ያልሽ እንደሆነ “እንዴት ነበር የምታደርጉት፣ ደሃ አታበሉም ነበር” ሲሉ ይጠይቁኛል።
እኔም የነበረውን ሁሉ አስረዳቸዋለሁ፡፡ የመንግስቱ ጥፋት አንዲት ናት፡፡ ሰውን ካለፍርዱ መግደሉ፤ “ለፍርድ ይቅረብ፣ ፍርድ ያውጣው ቢል” ጥሩ ነበር። እሱ ጥሩ ሰው ነው፤ በዙሪያው ብዙ ቀጣፊዎች ነበሩ የሚያሳስቱት፡፡ ደሃ ሲያይ ይጨነቃል፤ ሀሰት አይወድም። አንድ ቀን ግቢውን ሲጎበኝ ጠራኝ… የብርቱካን ልጣጭ ወድቆ አይቶ… “በሉ የሚመለከተውን ሰው ጥሩና ይሄን አፅዱ አለኝ” አንቱ ብሎ፡፡ ሰውን አክብሮ ነው የሚናገር።
በኢህአዴግ ዘመንስ ቤተመንግሥት ሰርተዋል?
ሁለት ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ ብዙም አያዙኝም ነበር። እንደገቡ ፍራሹን ከየክፍሉ አወጡ አሉን፡፡ ለወታደሩ መተኛ አሰናዳን፡፡ መለስ እንደ ኃላፊ ሆኖ መጣ፤ በኋላ ከፍ አደረጉት፡፡ ብዙ ጊዜም ያነጋግረኝ ነበር፡፡ “አጥሩን… በሩን እንደዚህ ያድርጉ፤ የጎደለብዎትን ለእኛ አለቃዎ ይንገሩ” አሉኝ፡፡
አሁን ጡረታ ስንት ያገኛሉ?
400 ብር አገኛለሁ፡፡  
በጡረታ ከቤተመንግስት ከተሰናበታችሁ በኋላ ባልደራስ የቤተመንግስት ጡረተኞች በሚል አንድ ትልቅ አዳራሽ ተከራይታችሁ ምግብ ቤት ከፍታችሁ ነበር…
ሁላችንም በጡረታ ተገለልን፡፡ ባልደራስ ጄነራል ፍሬ ሰንበት የተማረ ልጅ ነው ፓይለት፡፡ ጃንሆይ ናቸው ያመጡት፤ እልፍኝ አስከልካያቸው ነበር… ይወደኛል፡፡
እና “ሆቴል ማቋቋም ፈልገናል፤ ከእኔ ጋር ብትሆን” አለኝ፡፡ አቋቋምንና ሰርግ መስራት ጀመርን፤ ጥሩ ሆነ። ጀነራልም ሞተብኝ… እኔም ደከም ስላልኩ ወጣሁኝ፡፡ አሁን በቤቴ ውስጥ ነው ያለሁት ልጄ፡፡
አንዴ እዚህ ባልደራስ ለሠርግ ተጋብዤ መጥቼ ነበር። ከምግብ አቀራረብና መስተንግዶ ስርዓቱ ጀምሮ እስከ ምርቃቱ ድረስ ለየት ያለ ስርዓት ነበረው፤ ከየት የመጣ ሥርዓት ነው?
ባልደራስ ማለት የጃንሆይ የበቅሎው፣ የፈረሱ ሃላፊ ማለት፡፡ በቤተመንግስት ውስጥ ያለውን ስርዓት ነው በሰርጉም ያየሽው፡፡ ሞሰቡ ሁሉ ቀሚስ ለብሶ ለብሶ ይመጣል፤ ወደ ግብር፡፡ ጃንሆይ በዚህ ስርዓት ጊዜ ይቆማሉ፡፡ ሞሰቡ “እንጀራ ይስጣችሁ፤ እንጀራ ይስጣችሁ” እየተባለ ያልፋል፡፡ አዛዡ አደግድጎ አሸብርቆ ነው፡፡ ለመኳንንቱ በመሶብ ነው የሚቀርብ። ያም ሲሆን ደግሞ በየማዕረጋቸው ነው፡፡ የአንቺን መቀመጫ የሚቀመጥበት የለም፡፡ በእኔ መቀመጫ የሚቀመጥ የለም፤ ይሄ ህጉ ነው፡፡ ከ4-6 ሰው በአንድ መሶብ ከብቦ ይበላል፡፡ እየተፈተፈተ አሳላፊው ያስተናግዳል፡፡ ጃንሆይ “የመኳንንቱን ምግብ አምጣው እስኪ” ብለው መሶቡን ያዩታል፡፡ በመሶቡ ላይ የተቀመጠውን እንጀራ ሰቅ ሰቅ ያደርጉታል፡፡ ይህን የሚያደርጉት አሳንሰውት እንዳይሆን በሚል ነው፡፡ “እንዴት ነው ደህና አድርገህ አጥቅሰሃል?” ብለው በእጃቸው ያያሉ፡፡ በአንድ ሞሰብ ከ20-30 እንጀራ ይቀርባል፡፡ የተረፈው የአሽከር መጫወቻ ነው፡፡ ጃንሆይ በክብራቸው በነ ራስ አበበ፣ በነ ቢትወደድ መኮንን እነ ራስ መስፍን… በጠረጴዛ ዙሪያ ይበላሉ፡፡ ሰርግ ላይ ያየሽው ስርዓት ከቤተመንግስት የመጣ ነው፡፡


Published in ህብረተሰብ

የሁለት ታላላቅ ግድቦች ወግ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ እና ታላቁ ‹‹ሁቨር ዳም››

   የህዳሴው ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 3ኛ ዓመት ሲከበር፤ ከስድስት ወር በፊት በአሜሪካ በነበረኝ ቆይታ የተደነቅሁበትን የሁቨር ግድብ አስታወሰኝ፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን የገባንበት ያህል ችግርና ውድቀት ባይገጥማቸውም፤ አሜሪካዊያን ያኔ በ1923 ዓ.ም ከባድ ቀውስና ጭንቀት ውስጥ ነበሩ። እኛ ከስልጣኔ ማማ ላይ ሳናውቀው ተንሸራተትን ከወደቅን ወዲህ፣ ለሺ አመታት ከከበበን ድቅድቅ ጨለማ ለመገላገል ስንመኝ ኖረናል፡፡ ጥንታዊውን የስልጣኔ ጉዞ እንደገና የሚያድስና የብልፅግና ዘመንን የሚያበስር ነገር እንፈልጋለን - የህዳሴ ግድብ ትርጉምም የዚህን ያህል ግዙፍ ነው - ‹‹ታላቅ ነበርን፤ ታላቅም እንሆናለን›› እንዲሉ፡፡
የሁቨር ግድብም እንዲሁ ለአሜሪካውያን ተቀራራቢ ትርጉም አለው፡፡ እስከ 20ያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ድረስ ለመቶ አመታት በስልጣኔና በብልጽግና ጐዳና ታይቶ የማይታወቅ ታሪክ የሰራችው አሜሪካ፣ ብዙም ሳይቆይ ነው በታላቅ የኢኮኖሚ ቀውስ የተመታችው፡፡ የ1920ዎቹ ዓመታት ለአሜሪካ ክፉ ዓመታት ናቸው፡፡ ብርሃኗ የደበዘዘባት፤ ፋና ወጊ መንፈሷ የቀዘቀዘባት ዘመን!
የረሃብና የግጭት አዘቅት ውስጥ ባይዘፈቁም፤ የስልጣኔና የብልጽግና ጉዟቸው ተብረክርኮ፤ የ‹‹ይቻላል›› መንፈስ የተዳከመባቸው አሜሪካዊያን፣ የጨለማ ድባብ ሲያንዣብብባቸው ጊዜ ህዳሴ አስፈለጋቸው፡፡ “ሁቨር ዳም” የዚያ ፍላጎት ውጤት ነው፡፡ በትግል ቋንቋ እንግለፀው ቢባል፤ “ብሶት የወለደው ጀግናው የአሜሪካ ህዝብ” እንደማለት ነው! እኛ ለአባይ የዘፈንለትን ያህል አሜሪካዊያን ለኮሮላዶ ወንዝ አላዜሙም፡፡ ነገር ግን እኛ ለአባይ ስንቆጭ እንደኖርነው፤ እነሱም በኮሮላዶ ወንዝ መቆጨታቸው አያጠራጥርም፡፡
ወንዙ ከአፍንጫቸው ስር እንደ ጅብራ ተገትሮ ሳይጠቀሙበት መፍሰሱ ሳያንስ፤ በየአመቱ ገጠር ከተማውን ሲያማርጥ በጐርፍ ያጥባቸዋል፡፡ በሸለቋማው ወንዝ፣ ከፍቅረኛው ተለያይቶ የቅርብ ሩቅ ለመሆን የተገደደ ጎረምሳ፤ “አንቺ ከአባይ ማዶ” እያለ እንደሚያንጎራጉረው ሁሉ፣ የኮለራዶ ወንዝም አሜሪካያውንን ሲያራርቅ ኖሯል፡፡
አሪዞናን ከወዲህ ማዶ፣ የኔቫዶ በረሃን ወዲያ ማዶ ሰንጥቆ የሚያልፈው የኮለራዶ ሸለቋማ ወንዝ፤ በርካታ ግዛቶችን እያቆራረጠ ይገሰግሳል፡፡ ዛሬ ግን እልም ካለው የኔቫዳ በረሃ ላይ ጉብ ካለችው ሽቅርቅሯ ላስ ቬጋስ ከተማ፣ ወደ አሪዞና በሚወስደው ምቹ መንገድ በመኪና ለሰላሳ ደቂቃ እንደተጓዙ፤ ፊት ለፊት ከአይንዎ ጋር የሚጋጨው ተራራና ገደል ሳይሆን ሰማይ ጠቀስ ግድብና ድልድይ ነው፡፡
በኦሪዞና ግዛት የፊኒክስ ከተማንና በኔቫዳ ግዛት ላስ ቬጋስን የሚያገናኘው ሰማይ ጠቀስ ድልድይ በየእለቱ በሰዎች ሲጥለቀለቅ ይውላል፡፡ “ከወንዝ ማዶ ያለሽው” እና “ከወዲያ ማዶ ያለኸው” እያሉ ናፍቆታቸውን የሚያንጐራጉሩ ፍቅረኞች አይደሉም በድልድዩ የሚተላለፉት፡፡ ሁቨር ዳምን ለማየት የሚመጡ ጐብኚዎች፣ እንጂ፡፡ ግድቡን ለመመልከት በየቀኑ የሚመጡ በርካታ ሺህ የዓለም ጐብኝዎች ረዥሙን ግድብ ላይ ላዩን አይተው አይመለሱም፤ ውስጥ ለውስጥም ይጐበኙታል፡፡ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ የሚገኙት ከግድቡ ስር መሬት ውስጥ በጥልቅ ቦታ ነው፡፡ በሊፍት ወደ መሬት ውስጥ ቁልቁል ብዙ ርቀት መግባት ያስፈልጋል፡፡
ሊፍት ከመያዛችን በፊት ከአስጐብኛችን አንደበት የወጡ ቃላት ፍርሃት ለቀቁብኝ፡፡ “ከመሬት በ5ሺህ ጫማ ርቀት ወደ ታች እንዘልቃለን፡፡ ይህ ግድብ ሲገነባ የዘጠና ስድስት ሰዎች ህይወት አልፏል” አለች፡፡
“አውቃችሁ ግቡበት” አይነት አባባልዋን እየሰማን በዝምታ ስንተያይ፤ እሷ በጣቷ የሊፍቱን መቆጣጠሪያ ተጫነች፤ ወደ መሬት እንብርት ይዞን እንዲሸመጥጥ፡፡ እንጀራዋ ነው፡፡ እንደ ባልደረቦቿ ጐብኚዎችን በቡድን እያሰባሰበች ስታስተናግድ ትውላለች፡፡ ከአንድ ሰዓት በላይ በሚፈጀው መስተንግዶ፤ በቀን አምስት ጐብኚ ቡድኖችን ተቀብላ ዙሪያውን ታስቃኛለች፡፡ ሰማይ ጠቀስ ግድቡንና ድልድዩን፤ እንደ አገር የተንሰራፋውን ሃይቅና ዙሪያ ገባውን ካስጎበኘች በኋላ፣ ነው የሃይል ማመንጫ ጣቢያውን ለማሳየት ቁልቁል ከአንድ ኪሎሜትር ጥልቀት በታች ይዛን የጠለቀችው፡፡ ወደ ምድር ስር የሚዘልቅ ባለ ሦስት መቶ ፎቅ ያህል እንደማለት ነው፡፡ ሳስበው አሁን ድረስ ያስፈራኛል። ከላያችን ላይ ግዙፍ ግድብ ብቻ ሳይሆን ግዙፍ ሃይቅ አለ፡፡ እዚያ ስር ነው፤ በየአመቱ 4.5 kwh የኤሌክትሪክ ሃይል የሚመነጨው፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላላ አመታዊ የኤሌክትሪክ ሃይል ከአንድ ግድብ ይመነጫል፡፡
በየአመቱ የ18 ሚሊዮን አሜሪካዊያን መኖሪያ አካባቢዎችን በጐርፍ እያጥለቀለቀ ከፍተኛ ጥፋት ሲያደርስ የነበረው ኮሎክራዶ ወንዝ፤ ዛሬ ለሚሊዮኖች የኤሌክትሪክና የብርሃን መፍለቂያ፤ ለሚሊዮኖች የመጠጥና የመስኖ ውሃ አስተማማኝ ምንጭ ሆኗል፡፡ እንደ አገር የሚሰፋው ሰው ሰራሽ ሃይቁም በዓለም ላይ የመጀመሪያው ትልቁ ሰው ሰራሽ ሀይቅ በመባል በመዝናኛነቱ ለመታወቅ በቅቷል፡፡ ነገር ግን፣ ግንባታው አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ለግድብ ግንባታ ተስማሚ የሆነ ቦታ ስላልተገኘ፣ የወንዙን አቅጣጫ ማስቀየር የግድ ነበር፡፡ የስራው ክብደት ራሱን የቻለ ፈተና ነው፡፡ ከሁሉም በፊት ግን የይገባኛል ውዝግቦችን በድርድር መፍታትና መስማማት ያስፈልግ ነበር፡፡ በርካታ ግዛቶችን የሚያካልለው ትልቅ ወንዝ፣ አቅጣጫውን እንዲቀይር ሲደረግ፤ በውሃ ክፍፍልና ድርሻ ላይ ከየግዛቱ ክርክሮች ተፈጥረዋል፡፡ እንዲያውም ውዝግቡ ከመካረሩ የተነሳ፣ የግድቡ ግንባታ ‹‹ህልም ሆኖ ይቀራል›› እስከመባል ደርሷል፡፡
ደግነቱ ስልጡን ሰዎች፣ እድሜ ልክ እየተወዛገቡ አይቀጥሉም፡፡ ይወያያሉ፤ ይደራደራሉ፡፡ ለዚህም ነው፤ የአሜሪካ 31ኛው ፕሬዚዳንት ኸርበርት ሁቨር ከየግዛቱ አስተዳዳሪዎችና ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት ሚዛናዊ የውሃ ክፍፍል እንዲኖር የተወያዩት፡፡ አስጐብኚያችን ከ90 አመት በፊት ስለነበሩት ፕሬዚዳንት ስትናገር፤ የአጐቷን ታሪክ የምትተርክ ትመስላለች፡፡
“ኸርበርት ሁቨር ከፖለቲከኛነቱ በተጨማሪ መሃንዲስ ነው፡፡ ወግ አጥባቂ ቢሆንም ደግ ሰው ነው፡፡ የታታሪነቱ ያህል አሳ በማጥመድ መዝናናትን የሚወድ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ‘የሰው ልጅ በአካባቢው የሚገኙ ተፈጥሯዊ ነገሮችን ወደ መልካምና ጠቃሚ ነገር የመለወጥ ችሎታ አለው’ የሚል ጠንካራ እምነትና ራእይ የያዘ ሰው ነው፡፡” … አስጎብኚያችን ፕሬዚዳንቱን በቅርብ የምታውቃቸው ሆኖ ሰተማኝ፡፡
የሆነ ሆኖ በውይይቱ ወደ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነው፤ በአንድ በኩል ተራሮችን በድማሚት መናድና የወንዙን አቅጣጫ ማስቀየር፤ በሌላ በኩል በሸለቆ የተራራቁትን ተራሮችን ለማገናኘት የግድብ ግንባታ የተጀመረው፡፡
በሰው ልጅ ታሪክ ታላቁን ግድብ በመስራት እውቀትና ችሎታቸውን ለማሳየት የተዘጋጁት አሜሪካዊያን መሃንዲሶች ከፈተና አላመለጡም። የኔቫዳ በረሃ፣ የኛው ህዳሱ ግድብ ከሚገነባበት ከቤኒሻንጉል ክልል ባልተናነሰ የሙቀት መጠን የሚታወቅ ቦታ እንደመሆኑ፣ ለግዙፍ የኮንክሪት ስራ በፍፁም አይመችም፡፡ የፎቅ ግንባታ ላይ እንደሚታየው፤ ቀጫጭን ምሰሶዎችና ግድግዳዎችን በኮንክሪት መስራት አያስቸግርም፡፡ ትንሽ ውሃ ከተረጨበት ኮንክሪቱ ብዙም ሳይቆይ ይቀዘቅዛል። ግራና ቀኝ፣ ፊትና ኋላ፣ ላይና ታች የተደፈነ የኮንክሪት ተራራ ሲገነባ ግን፣ ኮንክሪቱ በፍጥነት የመቀዝቀዝ እድል የለውም፡፡
ኮንክሪቱ እስኪቀዘቅዝ እየጠበቀን እንስራ ከተባለ ግንባታው 100 ዓመት እንደሚፈጀ ነበር የተገመተው፡፡ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ኮንክሪቱ እንዲቀዘቅዝ የሚደረገው ላዩ ላይ በረዶ በማፍሰስ ነው፡፡ የሁቨር ግድብ ሲገነባ ግን፣ እንደዛሬ በረዶ ማምረቻ ማሽን በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም፡፡ ቢሆንም መሃንዲሶቹ ውሃ በመጠቀም ኮንክሪቱን የሚያቀዘቅዝ መላ ዘየዱ፡፡ ስራውም ሳይጓተት ቀጠለ፡፡ እንዲያውም ሰባት አመት ይፈጃል የተባለው ግንባታ ከታቀደለት ጊዜ ቀደም ብሎ በአምስት ዓመት ተጠናቀቀ፡፡  
ግድብ ለመስራት የፈሰሰው ሲሚንቶና ኮንክሪት፤ 4674 ኪሎ ሜትር ደረጃውን የጠበቀ ሰፊ የአስፓልት መንገድ ሊሰራ ይችላል፡፡ ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ የሚዘልቅ አስፋልት መንገድ ማለት ነው፡፡ በምን ያህል ወጪ እንደተገነባ አትጠይቁኝ፡፡
ለካ በኛ አገር ብቻ ሳይሆን በአሜሪካም፣ ያኔ ድሮ ሁሉም ነገር ርካሽ ነበር፡፡ ለግድቡ የወጣው ገንዘብ 49 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በዛሬ ገንዘብ ቢሰላ ከቢሊዮን ዶላር ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ በሦስት ፈረቃ ተፍ ተፍ ለሚሉት 3500 አሜሪካዊያን ሰራተኞች የሚከፈለው ደሞዝ፤ እንደ የሙያቸው ቢለያይም፣ ዝቅተኛው ክፍያ በቀን አራት ዶላር ነበር፡፡ ቀላል ይመስላል፡፡ በዛሬ ሂሳብ ከ100 ዶላር ሊበልጥ ይችላል፡፡
አስተማማኝ የኤሌክትሪክና የውሃ ምንጭ ከመሆን አልፎ፣ ለበርሃማው አካባቢ አዲስ ሕይወት የሚሰጥ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ለመፍጠር የበቃው ግድብ ሲጠናቀቅ፤ ኸርበርት ሁቨር ስልጣን ላይ አልነበሩም። እንደመታደል ሆኖ የእኛው የቀድሞ ጠ/ሞኒስትር መለስ ዜናዊም የግድቡን የመሰረት ድንጋይ ጥለው ግንባታውን ቢያስጀምሩም መርቀው ለመክፈት ሳይታደሉ ህይወታቸው አልፏል፡፡
በኮሰራይ ወንዝ ላይ፣ በኛው ቋንቋ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታውን ያስጀመሩት ሁቨር፤ የስልጣን ዘመናቸው በምርጫ ተቋጭቷል። በምትካቸው ስልጣን የተረከቡት ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 30ቀን 1935 ዓ.ም ግድቡን መርቀው ከፈቱት። “ቦልደርስ ዳም” ነበር የሚባለው፡፡ ስሙ የተለወጠው በ1947 የአሜሪካ ኮንግረስ ሁቨር ዳም ተብሎ እንዲሰየም ባሳለፈው ውሳኔ ነው፡፡ የኛ ግድብ ግን፣ ገና ሳይጀመር ነው ስሙ የተለወጠው፡፡ “ሚሌኒየም ግድብ” የሚለው ስያሜ ተቀይሮ “ህዳሴ” ግድብ ተብሎ የተሰየመ፡፡     
  አስጎብኛችን በመሬት ውስጥ ቆይታችን የአስራ ሁለት ደቂቃ ትንተናዋን ጨርሳ ወደ ምድር ወለል ለመውጣት ሽቅብ ስንገሰግስ ፍርሃቴ አላገረሸም። ‘አንድ ነገር ቢመጣኮ እዚሁ ድፍት ብለን መቅረታችን ነው’ የሚለው ስጋቴ ለቆኝ ወደሌላ ሃሳብ ተጉዣለሁ። ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ!!  
የህዳሴው ግድብ ምርቱ ተትረፍርፎ፣ በድርቅና በረሃብ ለምትታወቀው አገራችን የጥንት ስልጣኔዋ እንዲታደስና የብልፅግና ዘመን እንዲበሰር ያደርግ ይሆን? የአገራችንን ገፅታ ይቀይር ይሆን? ግንባታው ሲጠናቀቅና እልፍ አእላፍት ሲጐበኙት፤ ኤሌክትሪክ ሲያመነጭና ለመስኖ ሲያገለግል ማየት ናፈቀኝ፡፡
“ይሁን!!” ብያለሁ፡፡ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ከአገር አልፎ ለጎረቤትም ያብራ!! ለመብላት የሚዘረጉ እጆች፣ ከአንድም ሶስት ጊዜ ጦም አይደሩ!! ስደትንና ድርቅን ያስወግዱ!!

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው በማያውቀው ነገር ባለቤቱ ማኩረፍ ትጀመራለች፡፡ ምክንያቱን ለማወቅ ቢሞክርም ነገርዬው ጭራሽ እየባሰ ቤት ውስጥ እሱን ማናገር ሁሉ ታቆማለች፡፡ ምን የሚያስቀይማት ነገር እንደሠራ ለማወቅ ቢሞክር አንዲትም ነገር ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ለቅርብ ወዳጆቹ ያማክራቸዋል፡ እነሱም ነገሩን ሲያጣሩ ለካስ የእሱው የቅርብ የሚባል ዘመድ እዚሀ ላይ የማይጻፉ ነገሮች እንደሚያደርግ በጎን ለሚስቱ ሹክ ይላት ነበር። ነገርዬውን ለሚስቱ በደንብ አስረድተዋት እርቅ ወረደ፡፡ ዘመድዬው ለምን እንደዛ ማድረግ እንደፈለገ እስካሁን ሊያወቁ አልቻሉም፡፡
እናላችሁ ዘንድሮ ሉሲፈር በሩቅ ባዳ ሳይሆን በቅርብ ዘመድ በኩል ይመጣባችኋል፡፡
የምር ግን…ሉሲፈር መልኩን እየለዋወጠ መከራችን እያበላን ነው፡፡ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…አለ አይደል… ሉሲፈር ያለገደብ እየፈነጨባት ያለች አገር ብትኖር የእኛዋ ነች፡፡ በስንትና ስንት በኩል ይመጣባችሁ መሰላችሁ!
ሉሲፈር፣ ሚኒስከርት በለበሰች እንትናዬ ተመስሎ ይመጣባችኋል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ! በባዶ አንጀት፣ በደከመ ጉልበት ምናምን እንደገና ሚኒስከርት አይተን!
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እንዴት ነው ነገሩ! ለእንትናዬዎቻችን ኮድ ተሰጣቸው እንዴ! አሀ…ወዳጆቼ የነገሩኝን ነዋ! ልክ ነው እንደ መኪና ታርጋ ለእነሱም ‘ኮድ ሁለት’፣ ‘ኮድ ሦስት’ እየተባለ መለያ ይሰጣቸዋል አሉ፡፡ እንግዲህ እኔ የማውቀው ‘ኮድ ሁለት’ የቤት ‘ኮድ ሦስት’ ደግሞ የንግድ ምናምን መሆናቸውን ነው። ጥያቄ አለን…ኮድ አሰጣጡ የሚመነዘረው በቃል በቃል ትርጉም ነው ወይስ በአዛማጅ ትርጉም!
ስሙኝማ…የምር ሳስበው ግን…አለ አይደል… ‘ኮድ ሁለት’ እያነሰ ‘ኮድ ሦስት’ እየበዛ የሄደ ይመስለኛል፡፡ (እነ እንትና… “ይመስለኛል” ማለትን እንኳን ተዉልና!)
ኮድ አሰጣጡ ይስፋፋልንማ… ‘የዕለት’፣ ‘ተላላፊ’ ምናምን የሚባሉ መለያዎችም ይካተቱልን። አያሻሙማ! በዕለቱ ‘ማሳካት’ ካልቻልን ዕድላችን እንደ ቤት ካርታ እንደሚመክን ብናውቅ አሪፍ ነዋ! ቂ..ቂ…ቂ…
‘ተላላፊ’ እስከዚህ ችግር የለበትም፡፡ “ጠዋት ተቀብተሽው የነበረው ሊፕስቲክ ምን አጠበው!” “ጋላክሲ 4 በየትኛው ገንዘብሽ ነው የገዛሽው!” ምናምን ብሎ ንትርክ አይሠራም፡፡ ኮዱ ‘ተላላፊ’ ይላላ! ቂ…ቂ…ቂ…
ሉሲፈር በ‘ቦተሊከኛ’ ተመስሎ ሊመጣ ይችላል። ልክ ነዋ…የዘንድሮ ‘ቦተሊከኛ’ ማጣፊያው ሲያጥረው፣ (“ሊበራልና ኒኦ ሊበራል ምንና ምን ናቸው?” የሚለውን መመለስ ሲያቅተው ማለትም ይቻላል! ቂ…ቂ…ቂ…) በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ወደ ስድብና ወደ “ዋ! ውርድ ከራሴ” አይነት ነገር ይገባል፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር የሚያሳስባችሁ ቦተሊከኛ ሞልቷል፡፡
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ድሮ፣ ድሮ ሴራው ሁሉ…አለ አይደል… የኢምፔሪያሊስቶች፣ ፔትሮ ዶላር ያሰከራቸው፣ የትሮትስካይቶች፣ የአምስተኛ ረድፈኞች፣ የፊውዳል ርዝራዦች… ምናምን ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ሴረኞች ወደ ‘ኒኦ ሊበራሊስቶች’ እየተጠቃለሉልን ስለሆነ ተመችቶናል፡፡ ልክ ነዋ…ትንፋሽና ቃላት እንቆጥባለና!  ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞላችሁ…ሉሲፈር በኃይማኖት ሰባኪ ተመስሎ ሊመጣ ይችላል፡፡ ልክ ነዋ…የመንግሥተ ሰማያትን ቋንቋ በሚያምር አንደበት እያንበለበሉ ስምንት የህይወት ዘመናት እንኳን ቢኖሩ ተናዘው የማይጨርሱት ሀጢአት ተሸክመው… አለ አይደል… “የመንግሥተ ሰማያት ‘ማስተር ኪይ’ በእኛ እጅ ነው…” የሚሉ ‘ኃይማኖተኞች’ መአት ናቸው፡፡ እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የእኛ ህዝብ ነገር ሆኖ ነው እንጂ ኃይማኖትን ለመባረኪያነት ሳይሆን ለመክበሪያነት የሚጠቀሙ፣ በሰማያዊ ቃላት ጀርባ የተሸሸጉ መአት ናቸው፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር የሚያሳስባችሁ ኃይማኖት ሰባኪ ሞልቷል፡፡
ሉሲፈር በሬስቱራንት አስተናጋጅ ተመስሎ ይመጣባችኋል፡፡ በዛ ሰሞን አንድ ሬስቱራንት ውስጥ ደስ ሳይለው የታዘዘ አስተናጋጅ ሱሪውን ሳይሆን በስህተት የትራስ ልብሱን ለብሶ የመጣ ነው የሚመስለው፡፡ ጨርቅ ይህን ያህል ይጨማደዳል! የምር እኮ…አጥቦ አስጥቶ እሲኪደርቅ ከሚወስደው ጊዜ ይልቅ መተኮሱ የበለጠ ጊዜ ይፈጃል! (ባለ ምግብ ቤቶች… የጠረጴዛ ጨርቅ ማሳመር ብቻ አይደለም!)  
ማስቲካ እያኘከች ትእዛዝ የምትወስድ፣ እጁን ኪሱ ከትቶ “ምን ይምጣ!” ብሎ የሚቆጣ፣ ምን ልታዘዝም ምን ይምጣም ሳይል አፍጦ የሚያይ፣ የማታዋን ጠጅ ለማምከኛ የሹሮ ፍትፍት ሳይበላ የመጣ (ቂ…ቂ…ቂ…)…ምን አለፋችሁ… ‘ትራጂያዊ ኮሜዲ’ (የሚባል ነገር አይጠፋም ብዬ ነው!) ምናምን ፊልም ሊሠራባቸው የሚችሉ በየቦታው አሉላችሁ፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር የሚያሳስባችሁ አስተናጋጅ ሞልቷል፡፡
እኔ የምለው የምግብ ቤት ነገር ከተነሳ አይቀር…  የአንዳንዶቻችን አበላል… አለ አይደል… ምን ይመስላል መሰላችሁ… ‘ላስት ሰፐር’ ይመስላል።  እንዴት ነው ነገሩ… ሁለት ጉንጭ ሞልቶም፣ ጮክ ብሎ አውርቶም ይሆናል እንዴ! ‘ቴብል ማነርስ’ የሚባለው ነገር ለ‘ሹካ’ ምግቦች ብቻ ሳይሆን ለቋንጣ ፍርፍርም እንደሚሠራ ግንዛቤ ይግባልንማ!
ሉሲፈር፣ በሚኒባስ ሹፌር ተመስሎ ይመጣባችኋል፡፡ በቀደም ከአምባሳደር ወደ አራት ኪሎ የሚወስደው ታክሲ ውስጥ ተቀምጠናል። እናላችሁ…ሁለት ተለቅ ያሉ ሰዎች እየገቡ እያሉ ሹፌሩ መኪናዋን አንቀሳቀሰና ሊወድቁ ተንገዳገደው እንደምንም ገቡ፡፡
ከዛላችሁ… አንደኛው ሰውዬ እንደ ቀልድም አስመስለው “ጥለኸን ነበር እኮ…” አሉት፡፡ እሱዬው ምንም መልስ አልሰጠም፡፡ ጭራሽ ሌላኛው ሰውዬ “አስቆጣነው መሰለኝ” አሉ፡፡ እሱ ሆዬ “ይቅርታ የለ፣ ምን የለ መንገዱን ቀጠለ፡ እናላችሁ በዛ ሰዓት ‘ሰይጣን ያሳሳተው’ ሰው “አይተህ አትነዳም!” ምናምን ቢል የሚፈጠረው ይታያችሁ፡፡ እናላችሁ…በስርአት ሳይነዳ ቀርቶ ላንገዳገደን የሚኒ ባስ ሹፌር ይቅርታ ጠያቂዎች እኛው ልንሆን ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሚኒባስ ሾፌሮችና ረዳቶች ባህሪይ… “ስደተኞችን ጭኖ ወደ የመን የሚሄደውን ጀልባ በየት በኩል ብሄድ አገኘዋለሁ?” ለማስባል ምንም አይቀረው። በየዕለቱ የማያቸው ነገሮች… “ይሄ ምስኪን ህዝብ በስንቱ መከራውን ይይ!” የሚያሰኝ ነው፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር የሚያሳስባችሁ ታክሲ ሾፌር ሞልቷል፡፡
ሉሲፈር ስልጣኔ አናታቸው ላይ በወጣ ወላጆች ተመስሎ ይመጣል፡፡ የምር አሥራ ሦስቷን ሳይደፍኑ ሁሉንም ነገር የሚለምዱ ልጆች…ዋናዎቹ ችግር ፈጣሪዎች ገንዘብ ሁሉ ነገር የሚመስላቸው ወላጆቻቸው ነው፡፡
“ሀብትና ዕውቀት አይገኙም አንድነት፣” የሚሏት ነገር እንዴት አሪፍ አባባል ነች!
ስሙኝማ…በቀደም አንድ ከተማ ወጣ ያለ ‘ፖፑላር’ መዝናኛ ውስጥ ገና ሃያ ያልተጠጉ ወጣቶች የሚሆኑትን ነገር ላየ…አለ አይደል…ተስፋ ቢቆርጥ ምንም አይገርምም፡፡ በከተማችን ውስጥ በየቦታው የሚሰሙ ነገሮች ሁሉ አንዳንዴ እንደ ልብ ወለድ ነገርም የሚቃጣቸው ናቸው፡፡ የምር ግን ሉሲፈር ከሙሉ ጦሩ ጋር እየሰፈረ ያለበት የሚመስል ስፍራ ቢኖር እዛ አካባቢ ነው፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር የሚያሳስቧችሁ ብላቴናዎች ሞልተዋል፡፡
እናማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ ሉሲፈር ራሱ… “እንደው ስለ ነገረ ሥራችን ምን ታስባለህ?” ተብሎ ቢጠየቅ…አለ አይደል…ምን የሚል ይመስለኛል መሰላችሁ…  “አሁንስ አበዛችሁት!  እንደውም አይደለም ላሳስታችሁ ቀርቶ እኔ ራሴ እየፈራኋችሁ ነው…” የሚል ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ…ብዙዎቻችን እኮ ‘ቀላል አልባሰብንም!’
እናላችሁ…ፍጹም ቅዱስ እንደሆንን የምናስመስል ሰዎች…አለ አይደል…ራሱ ሉሲፈር ሊፈራን የሚገባን አይነት ነን፡፡ ሰውየው “ከወዳጆቼ ጠብቀኝ ጠላቶቼን እኔ እጠብቃቸዋለሁ…” ነው ምናምን አለ እንደተባለው ዘንድሮ ሉሲፈር ሰተት ብሎ የሚመጣው በወዳጅ በኩል ነው፡፡
ሉሲፈር በጥበቃ ሠራተኛ ተመስሎ ይመጣባችኋል፡፡ የሚገርም እኮ ነው…ለጥበቃ ሠራተኞች “ሰማይ አይታረስ፣ ንጉሥ አይከሰስ” አይነት ስልጣን በሰርኩላር ተላልፎላቸዋል እንዴ! አንዳንድ ጊዜ እኮ እዛ መሥሪያ ቤት የሄዳችሁት ለጉዳይ ሳይሆን እርጥባን ልትጠይቁ  ያስመስሉታል። ስሙኝማ… የአንዳንድ ጥበቃ ሠራተኞችን የ‘ንቀት’ አስተያያት ልብ ብላችሁልኛል… ምን አለፋችሁ… ከጫማችሁ ጀምሮ ‘ስካን’ ሲያደርጓችሁ ሥራ አስኪያጁ ዘንድ ወረቀት ለማስፈረም የምትሄዱ ሳይሆን ለርቢ የታጫችሁ ኮርማ ነገር ያስመስሏችኋል፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…”  የሚያስብል ነገር የሚያሳስባችሁ የጥበቃ ሠራተኛ ሞልቷል፡፡
ሌላውን “ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር እንዲያስብ የምናደርግ፣ ሉሲፈር ተንሰራፍቶ ለሽ ያለብንን ሁሉ አንድዬ ልቦናውን ይስጠንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
  • ባለ16 ሺ ብሩ ሞባይል ተመለሰ ወይስ ተወረሰ?
  • “ታላቅ ነበርን፤ ታላቅም እንሆናለን!”

    እንኳን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!! እናንተ… ጊዜው እንዴት ይከንፋል እባካችሁ… ህዳሴ ግድቡ ከተጀመረ ሶስት ዓመት ሞላው እኮ! ደግነቱ የግድቡም ሥራ የዚያኑ ያህል ስለከነፈ አይጨንቀንም፡፡ በነገራችሁ ላይ---በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ የህዳሴን ግድብ ቀን ከሌሊት በ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት (እሳት እኮ ነው!) እየተቀቀሉ የሚገነቡት ታላላቅ ባለሙያዎችና ሰራተኞች “የጦቢያ የቁርጥ ቀን ልጆች” የሚል ብሄራዊ ሜዳልያ መሸለም ይገባቸዋል፡፡ (እነሱ ለህይወታቸው ሳይሰስቱ እኛ ለሽልማት ልንሰስት?) ለአድናቆትና ለምስጋና ከሰሰትንማ ከግብፅ አልተሻልንም፡፡ (ምስጋና እንደ አባይ ውሃ፣ አያልቅም!!)
ዛሬ እንግዲህ ወጋችን ሁሉ በህዳሴ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ወጋችን ህዳሴ ነው ብለን ግን ከሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃ ውጭ በስሜት ተሞልተን መወራጨት አይፈቀድም፡፡ (ከህዳሴ ጋር አይሄድማ!) አንዳንዶች ለአገር ጥቅምና ለህዳሴ ግድብ ከሆነ፣መዋሸትም ማጋነንም መተርተርም ትክክል ይመስላቸዋል፡፡ ለአገር ጥቅም ከሆነ፣ ሰውን ማሰቃየትም ማዋከብም ማሰርም መፍታትም ማመናጨቅም ተገቢ ይመስላቸዋል፡፡ ግን ትልቅ ስህተት ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ደረሰብን ያሉትን ሰምታችሁልኛል - ወደ ቡታጅራ ግድም መሰለኝ፡፡ “ሞባይላችንን ወስደው ኬሚካል ነክረው መለሱልን” ነው እኮ ያሉት! (“ፀረ-ቴክኖሎጂ ሚሳይል” ይሏል ይሄ ነው!) ኢህአዴግ 30/70 እያለ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ መከራውን ይበላል፣የቡታጅራ ኢህአዴጎች ግን የ20 ተቃዋሚዎችን ሞባይል ኬሚካል ውስጥ ሲነክሩ ይውላሉ፡፡ (ሞባይሎቹን ከመስራት ወዳለመስራት ሲለውጧቸው ምን ተሰምቷቸው ይሆን?) ያደላቸውማ--- እለት ተእለት አዲስ የሞባይል ምርት ለመፍጠር ሲታገሉ ይውላሉ፡፡ የኛዎቹ ደሞ የተፈጠረውን ያወድማሉ፡፡ እኔ የምለው----ኬሚካል ውስጥ የተነከረባቸውስ እርማቸውን አውጥተዋል፡፡ እኔን ያሳዘነኝ ማን መሰላችሁ? የ16ሺ ብር ሞባይል የተወሰደበት አመራር! (ተመለሰ ወይስ ተወረሰ?) ቆይ ግን እሱ ብቻ ተመርጦ የት ተሰወረ? (እንፈልግ ብንል ደሞ እንደ ማሌዥያው አውሮፕላን ነው የሚሆንብን!)
 እናላችሁ----- የአገር ሰላም ለማስጠበቅ---- የጎዳና ነውጥ ለመከላከል----ህገወጥ ስብሰባ ለማክሸፍ---ወዘተ በሚል ሰበብ የሰው ንብረት ወስዶ ከጥቅም ውጭ ማድረግ እብደት እንጂ ጤንነት አይደለም፡፡ መቼም ኢህአዴግ “ሞባይላቸውን ቀምታችሁ ኬሚካል ውስጥ ክተቱት” አይልም፡፡ (ማን ነበር በየኪሳችን ውስጥ “ትናንሽ ዘውዶች” ይዘን ነው የምንዞረው ያለው?) የየክልላችን---የየወረዳችን----የየክፍለከተማችን- ----የየቀበሌያችን----ንጉስ መሆን እንፈልጋለን፡፡ (ዱርዬ ከመሆን ንጉስ ካልሆንኩ ብሎ መንጠራራት ይሻላል!) የሆኖ ሆኖ ግን ---- እንዲህ ያለው የማይረባ “ጉልቤነት” በህዳሴ ዘመን መሳቂያ እንጂ መኩሪያ አይሆንም!    
የህዳሴ ግድብ ምስጋና ይግባውና ---- ብዙ ነገሮች በህዳሴ ጎዳና ላይ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን አንዳንዶች የጦቢያ ህዝብ የሚዋደደው፣ጠላት ሲነሳበት ነው እያሉ ቢያሙንም ------ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የዘር ልዩነት ሳይከፋፍለን ለህዳሴው ግድብ በአንድነት መቆማችን፣ የዚህች ተዓምረኛ  አገር ለዘመናት ተከብሮና ታፍሮ መኖር የማዕዘን ድንጋይ ይመስለኛል (አበሻ በአገሩና በክብሩ ወለም ዘለም አያውቅም!)
የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ለህዳሴ ግድብ ያሳየውን ህብረትና ትብብር ሳስብ ውስጤ በሃሴት ይሞላል። እናንተ---ኢህአዴግ ዝም ብሎ ደከመ እንጂ አበሻ በሙሉ እኮ ልማታዊ ነው፡፡ እናም ከአሁን ወዲህ ብዙ ፕሮፓጋንዳ አያስፈልገንም (የካድሬ እጆች ለልማት ይዋሉ!) ይኼውላችሁ----ድሮም እኮ ልማት የሚጠላ ህዝብ የለም (“በልፅጉ!” ብሎ ፕሮፓጋንዳ አለ እንዴ?) ከምሬ እኮ ነው… ጠግበህ ብላ፣ ኪስህ ይሙላ፣ ተደላድለህ ኑር፣ በሃብት ተንበሽበሽ… እንዲህ ያለ ፕሮፓጋንዳ አያስፈልግም እኮ፡፡ (ብልፅግና የማይፈልግ የለማ?) ልማትን መሻት፣ ብልፅግናን ማለም… የሰው ልጅ ተፈጥሮ እኮ ነው!! የሚያስፈልገው ምን መሰላችሁ? መንገዱን ክፍት ማድረግ! ተሰርቶ የሚበለፅግበትን ክህሎት ማስታጠቅ! የቢሮክራሲ ሰንሰለትን መበጣጠስ፡፡ ነገር የሚበላሸው መቼ መሰላችሁ? ልማቱ ፖለቲካ ሲሆን ነው፡፡ አዎ ልማቱ ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሲሆን “አደጋ አለው!” (ወሬና ዲስኩር አይመነዘርማ!)
አያችሁ… ልማታዊ ትያትር፣ ልማታዊ ጋዜጠኝነት፣ ልማታዊ ባለሃብት፣ ልማታዊ መምህር ወዘተ .. የሚሉት ፍረጃና ክፍፍል ለጦቢያ አይጠቅማትም፡፡ ኢህአዴግ መፈረጅ ይወዳል እንጂ ጦቢያ ውስጥ ሁሉም ልማታዊ ነው (ኢህአዴግ ነው ማለት ግን አይደለም!) እናላችሁ… የኢህአዴግ ካድሬዎች 20 ዓመት ሙሉ “ልማታዊ… ልማታዊ” ብለው ያልፈጠሩትን ለውጥ፣ የህዳሴው ግድብ በ3 ዓመት ብቻ እውን አደረገው፡፡ ያውም ጦቢያን በሙሉ በአንድነት አስተሳስሮ!  ኢህአዴግ ነፍሴ አንድ እውነት እንዲረዳልን እንፈልጋለን… ድሮም ህዝቡ የጠላው ልማቱን ሳይሆን ዲስኩሩን ነው (ዲስኩር ዳቦ አይሆንማ!) ደሞም እኮ አይፈረድብንም፡፡ ደርግ 17 ዓመት ሙሉ ፕሮፓጋንዳ ሲግተን ነው የኖረው (ኢህአዴግ ሲጨመር አንገሸገሸን!)
እኔ የምላችሁ… ኢህአዴግ በሁለት አስርት ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ከእነመኖራቸውም ትዝ ብለውት የማያውቁትን የጦቢያን ምሁራን “ለአገራችሁ ታስፈልጋላችሁ!” ማለት መጀመሩን እንዴት አያችሁት?  ተዓምራዊ ለውጥ እኮ ነው! (ይሄም የህዳሴው መግነጢሳዊ ኃይል መሆኑን ልብ በሉልኝ!) እናላችሁ… የዩኒቨርሲቲ ኢንጂነሮችና ፕሮፌሰሮች ክፍል ውስጥ ከማስተማር ውጭ በግድቡ ግንባታ የአማካሪነት ሚናቸውን ይጫወታሉ ተብሏል፡፡ (ያካበቱትን ሙያ እየመነዘሩ!) ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ በዲፕሎማሲው ዘርፍም ብዙ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡ ግድቡን ማስተዋወቅና ተያያዥ ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ እስከዛሬም ቢሆን ኢህአዴግ ጥርቅም ያደረጋቸው እኮ … አብዛኛው ስራ ፖለቲካ ስለነበር ነው፡፡ (ብዙ ፖለቲካ፣ ትንሽ ልማት) አሁን ግን ዕድሜ ለህዳሴው ግድብ! … ነገሮች ተለውጠዋል! ጊዜው የሚፈልገው ዲስኩር ሳይሆን ዕውቀት ነው! ፕሮፖጋንዳ ሳይሆን ተግባር ነው! እስቲ አስቡት… ሁሉም በህዳሴው ኢንስፓየርድ ሆኖ----ግድቡ በሚገነባበት ፍጥነት በየሙያው ቢተጋ!(እነቴሌና መብራት ኃይልን አይመለከትም!) እንዴ --- ሁለቱም እኮ ብሶባቸዋል! ባለፈው ሳምንት ---- በአንድ ከሰዓት ብቻ ከሰባት ጊዜ በላይ መብራት ሄዶ መጥቷል -በየግማሽ ሰዓቱ!
በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ከህዳሴው ግድብ መጀመር በኋላ ብዙ የባህሪ ለውጥ እያመጣ ነው- ለራሱም ለአገርም የሚበጅ፡፡ ከዳያስፖራው ጋር ያለውን ግንኙነት እያሻሻለ ይመስለኛል (“ወዶ ነው!” ከሚሉት ወገን ግን  አይደለሁም!) ይልቁንም ይሄም የህዳሴው መግነጢሳዊ ኃይል ሌላ ማሳያ ነው.. ባይ ነኝ፡፡
በነገራችሁ ላይ … የህዳሴውን 3ኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክቶ ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስቴዲየም የሴት ባለሃብቶችና የአርቲስቶች ቡድን እንዲሁም የወንድ አርቲስቶችና የመንግስት ባለስልጣናት ቡድን ያደረጉት የእግር ኳስ ግጥሚያ ብዙዎችን አዝናንቷል (ዓላማውም እኮ እያዝናኑ ለህዳሴው ገንዘብ ማሰባሰብ ነበር!) ኮሜንታተሩ ግን የአርቲስቶችና የባለስልጣናትን ግጥሚያ ሲያስተላልፍ ደጋግሞ “የባለሥልጣናት ቡድን እየታለለ ነው---” ማለቱ አንዳንድ ባለስልጣናትን ማስቀየሙ አልቀረም (በሆዳቸው ማለቴ ነው!) እኔ የምለው----አምናም ዘንድሮም ለህዳሴው በተደረገው የእግር ኳስ ግጥሚያ ለምንድነው ተቃዋሚዎች ያልተሳተፉት? ሲሆን ሲሆን የመንግስት ባለስልጣናት ምድባቸው ከአርቲስቶች ሳይሆን ከተቃዋሚ አመራሮች ነበር (ምርጫ ላይ መጋጠማቸው ይቀራል?!) በዚህ በህዳሴ ዘመን አውራው ፓርቲ ከተቃዋሚው ጋር ተባብሮ መሥራት መጀመር አለበት፡፡ እውነቴን እኮ ነው… በአባይ ጉዳይ “ጠላት” ከሚባል መንግስት ጋር ለመስራት ጎንበስ ቀና እያልን አይደለም እንዴ!፡፡ ለግብፅ ማዳበሪያ ሙሉ ትዕግስት ካለን፣ እንዴት ለተቃዋሚ ወይም ለአውራው ፓርቲ አንድ ፌስታል ትዕግስት እናጣለን?
የገዢው ፓርቲና የተቃዋሚዎች ተግባብቶ መስራት እንደዋዛ የሚታይ ጉዳይ እንዳይመስላችሁ!! አዲሱ ትውልድ፤ የህዳሴውን ግድብ ተረክቦ ብቻ ይረካል ካላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ አዲሱ ትውልድ ጥያቄው ብዙ ነው- ስልጡን የፖለቲካ ባህሉስ? ሥር-መሰረት ያለው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱስ? የዳበረ ነፃ ፕሬስስ? የግል ሬዲዮና ቴሌቪዥኑስ? የዜጐች ሰብዓዊ መብት አከባበሩስ? ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነፃ የሆነ የፍትህ ሥርዓቱስ? ነፃና እንከን የለሽ የምርጫ ሂደቱስ?--- እኒህን ሁሉ እንደ ህዳሴው ግድብ በጥራትና ዓለምአቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየገነባን ነውን?? (ራሳችንን እንፈትሽ!)
ሰሞኑን በኢቴቪ ወይም በአዲስ አበባ መስተዳድር…የህዳሴውን ግድብ ሦስተኛ ዓመት አስመልክቶ፣ ሁለት አዝማሪዎችና አንድ እንስት ገጣሚ የተካተቱበት ዝግጅት ቀርቦ ነበር፡፡ በአባይ ዙሪያ ማሲንቆ እየተደረደረ ግጥሞች ተነበዋል። አርቲስቶቹ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሃሳብና አስተያየታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ ብልሁ ማሲንቆ ደርዳሪ ፕሮግራሙ ከመቋጨቱ በፊት መፍትሄ ያጣውን የዘፋኞች የኮፒራይት ጉዳይ ለማስታወስ ሞከረ-በተራ ቋንቋ አይደለም በግጥም ነው- በአዝማሪ ወግ!! በእርግጥ ግጥሞቹ  የጥራትና ደረጃ መዳቢን ማረጋገጫ ማለፋቸውን  አላውቅም፡፡) አንደኛው ግጥም እንዲህ ይላል፡-  
“ለጠየቅነው ሁሉ ካልተሰጠን ምላሽ  
አሁን ያስቸገረን ቪዲዮና ፍላሽ”
ወደ ሁለተኛው ግጥም ልውሰዳችሁ፡-
“ኦሪጂናል እያለ የሚገዛ ቅጂ
አድናቂ አይባልም አብሻቂ ነው እንጂ!”
የአዝማሪውን ግጥሞቹ ዝም ብዬ አልጠቀስኳቸውም (በየዘርፉ ብዙ ህዳሴዎች እንደሚቀሩን ለመጠቆም ብዬ ነው!)
ወጌን የምቋጨው ሰሞኑን በኢቴቪ በሰማሁት አንድ የምትመች አባባል ነው “ታላቅ ነበርን፤ ታላቅ እንሆናለን” (ጊዜው የህዳሴ ለመሆኑ ይሄም ጠቋሚ ነው!)በነገራችሁ ላይ ይሄን አባባል መጀመሪያ የሰማሁት በእነዘነበ ወላ የኤፍ ኤም 97.1 ፕሮግራም ላይ ነው (የኮፒራይት መብት ይከበር እንጂ!)


ኢቴቪ የማረሚያ ፕሮግራም እንዲያስተላልፍ ፍ/ቤት አዟል
“መልካም ስሜን የሚጠግን ተመጣጣኝ ፕሮግራም ሠርቼ አቀርባለሁ”

      የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  ባስተላለፈው “አኬልዳማ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም፣ መልካም ስሜን አጉድፏል ሲል አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤ኢቴቪን መክሰሱ የሚታወስ ሲሆን ሰሞኑን የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት በሰጠው ውሣኔ፣ ጣቢያው ቀደም ብሎ ለ“አኬልዳማ” በሰጠው የአየር ሽፋን መጠን የሚቀርብ፣ በፓርቲው ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያካክስ ፕሮግራም ሠርተው ያቅርቡ ሲል ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡
አንድነት በበኩሉ፤ በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት መልካም ስሜን የሚጠግን፣ተመጣጣኝ ፕሮግራም ሠርቼ አቀርባለሁ፤ ለደረሰብኝ የወጪ ኪሣራም ተገቢውን ካሣ እጠይቃለሁ ብሏል፡፡
ፍ/ቤቱ በሰሞኑ ውሣኔው ተከሳሽ (ኢቲቪ)፤ ከህዳር 16 እስከ ህዳር 18 ቀን 2004 ዓ.ም በጣቢያው ባስተላለፈው “አኬልዳማ” ዘጋቢ ፊልም፣ ከሣሽን  ከግንቦት 7 የሽብር መረብ አንዱ መሆኑን፣ አባላቱም ብጥብጥና ሁከት ፈጣሪ መሆናቸውን፣ ለአሸባሪዎች አመራርና አባላቱ ሽፋን እንደሚሰጡ በማመላከት ዘገባ ማቅረቡንና የፓርቲውን ስም ማጥፋቱን ጠቅሶ  ድርጊቱ አግባብ አይደለም ብሏል፡፡ በዚህም መሰረት ተከሣሽ ይሄንኑ ዘገባ በሚያርም መልክ ተመጣጣኝ ፕሮግራም በጣቢያው እንዲያስተላልፍ ወስኗል፡፡ ከሣሽ በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰበትን ወጪ ዘርዝሮ፣ ተከሣሽን ካሣ የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ እንደሆነም ፍ/ቤቱ ገልጿል፡፡
“ፍ/ቤቱ ለደረሰብን የሞራልና የቁስ ኪሣራ ካሣ መጠየቅ እንደምንችል በውሳኔው ስላመለከተ፤በዚህ መሠረት ተገቢውን ካሣ አስልተን እንጠይቃለን” ብለዋል- አቶ ሃብታሙ፡፡
በፍ/ቤቱ ውሣኔ ሙሉ ለሙሉ አለመርካታቸውን የገለፁት ሃላፊው፤“በተለይ በሽብር የተከሰሱት ግለሰቦች ጉዳያቸው በፍ/ቤት የተያዘ መሆኑ እየታወቀ፣ ከህግ አግባብ ውጭ በንፁህ የመገመት መብታቸውን ተነፍገዋል” ለሚለው የፓርቲው የክስ ነጥብ፣ ውሣኔ አለመሠጠቱ ቅር እንዳሰኛቸው ጠቁመው፤አሸባሪ የተባሉት ግለሰቦች ነፃ እስኪወጡ ድረስ የፓርቲው ትግል እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል አንድነት ፓርቲ መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚያካሂደው ሠላማዊ ሠልፍ ጋር በተገናኘ ከአስተዳደሩ ጋር አለመግባባት መፈጠሩንና ፓርቲው ያቀረባቸው ሶስት  አማራጭ  ቦታዎች ውድቅ መደረጋቸውን አቶ ሃብታሙ ጠቅሰው፣ አስተዳደሩ ሠልፉን ለማደናቀፍ  እየሞከረ ቢሆንም ፓርቲያቸው ሠላማዊ ሠልፉን ከማከናወን ወደ ኋላ እንደማይል ገልፀዋል፡፡   

Published in ዜና

        በአለም አቀፉ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የካበተ ልምድ ያላት አፍሪካ - አሜሪካዊቷ ኢትዮጵያ ሐብተማርያም፣ የታዋቂው የአሜሪካ የሙዚቃ ቀረጻ ኩባንያ የሞታውን ሪከርድስ ፕሬዚዳንት ሆና መሾሟን ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ ገለጸ፡፡ የአለማችን ትልቁ የሙዚቃ ኩባንያ የሆነው ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ፣ ከዚህ በፊት በስሩ ይተዳደሩ የነበሩትን ዴፍ ጃም ሪከርድስ፣ አይስላንድ ሪከርድስና ሞታውን ሪከርድስን እንደገና በማዋቀርና ራሳቸውን ችለው እንዲሰሩ በማድረግ፣ ኢትዮጵያ ሃብተማርያምን የሞታውን ሪከርድስ ፕሬዚዳንት አድርጎ በዚህ ሳምንት መሾሙን አስታውቋል፡፡እ.ኤ.አ በ2003 ታዋቂውን ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ የተቀላቀለችው ኢትዮጵያ ሐብተማርያም፣ ጀስቲን ቢበርና ክሪስ ብራውንን ጨምሮ አለማቀፍ ዝና ያላቸውን በርካታ ታዋቂ ድምጻውያን፣ የሙዚቃ ደራሲያንና አርቲስቶችን ለኩባንያው በማስፈረም ተጠቃሽ ስራ የሰራች ሲሆን፣ ከ2011 አንስቶም የዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የኧርባን ሚዩዚክ ሃላፊ በመሆን አገልግላለች፡፡
ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕን በምክትል ፕሬዚዳንትነት በመራችባቸው አመታት፣ ሜሪ ጄ ብላይጄ፣ ፊፍቲ ሴንት፣ ኤሚኔየም፣ አሻንቲ፣ አይስ ኪዩብ፣ አር ኬሊና ሌሎች በርካታ የፕላቲኒየምና የግራሚ ተሸላሚ አርቲስቶችን ወደ ኩባንያው በመሳብ፣ ስኬታማነቷን ያስመሰከረችው ኢትዮጵያ ሐብተማርያም፣ ለረጅም አመታት በዘርፉ ተጠቃሽ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየውን ሞታውን ሪከርድስ ወደተሻለ ትርፋማነት ታሸጋግራለች ተብሎ ስለታመነባት ነው በፕሬዚዳንትነት የተሾመችው፡፡
ሞታውን ሪከርድስ የማኔጅመንት፣ የማርኬቲንግና የማስታወቂያ ስራ አቅሙን የበለጠ በማሳደግ፣ ራሱን የቻለ አለማቀፍ የሪከርዲንግ ኩባንያ እንዲሆን ፣ ኢትዮጵያ ሐብተማርያም ከፍተኛ ሃላፊነት እንደተጣለባት የዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ መግለጫ ያሳያል፡፡
የዩኒቨርሳል ሚውዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሉቺያን ግሬንጅ እንደተናገሩት፣በኢትዮጵያ ሐብተማሪያም የሚመራው ሞታውን ሪከርድስ፣ ተቀማጭነቱን እ.ኤ.አ ከ1972 ጀምሮ ለ25 አመታት ያህል  በርካታ ስራዎችን አሳትሞ ለአድማጭ ሲያቀርብበት በነበረው ሎሳንጀለስ በማድረግ፣ በዘርፉ አያሌ  ስራዎችን ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ሐብተማርያም ከአዲሱ ሹመቷ በተጨማሪ፣ በዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ የኧርባን ሚዩዚክ ሃላፊነት ስራዋን ጎን ለጎን እንደምትቀጥል ተነግሯል፡፡

Published in ዜና

በህገወጥ መንገድ በኬንያ ድንበር ተሸግረው በታዛንያና፣ በማላዊና በሞዛምቢክ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር ሲሞክሩ በፖሊስ የተያዙት 200 ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ ሲሆኑ፤ በርካቶቹም በጉዞ እንግልት በከፍተኛ ህመም ደርሶባቸዋል፡፡
159 ኢትዮጵያውያን የታሰሩት በማላዊ ፓሊስ እንደሆነና የተቀሩት ደግሞ የኬንያን ድንበር ከመሻገራቸው በፊት በኬንያ ፖሊስ እንደተያዙ ታውቋል፡፡
ጫካና በረሃ እየቆራረጡ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ጉዞ በውሃ ጥምና በረሃብ በአውሬና በዘራፊ የብዙዎች ህይወት የሚቀጠፉበት በመሆኑ ሴቶች እንደማይደፍሩ የሚታወቅ ሲሆን፤ አሁን የታሰሩት 200 ኢትዮጵያዊያን ወንዶች ናቸው ተብሏል፡፡
ለህገወጥ ደላሎች ከ4ሺህ ብር በላይ በመክፈል በመክፈል ጉዞ ከጀመሩ ስደተኞች መካከል አንዳንዶቹ፣  የያዙት ገንዘብ በዘራፊዎች ተነጥቀው ስንቅም አልቆባቸው ቅጠላ ቅጠልና ሳር ለመመገብ መገደዳቸው ተገልጿል፡፡

Published in ዜና
Page 12 of 13