Saturday, 26 April 2014 13:05

አዋቂዎቹ

     ሊዮ ቶልስቶይ /Count Leo Tolstoy 1828-1910 እ.ኤ.አ የሩሲያ ንጉሣዊያን ቤተሰብ አባልነቱ ያስገኘለት እጅግ ሰፊ የእርሻ መሬት ባለቤት የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን፤እንደ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሰው ሊኖር የሚገባውን ዝቅ ብሎ የመኖር ግብር ለመፈፀም ሲል፤ሀብት ንብረቱን ሁሉ አሳልፎ ሰጠ፡፡ በድህነት የሚንከላወሱ ህጻናትንም የንባብ ፍቅር እንዲያድርባቸው ፊደል መቁጠር ያስተምራቸው ነበር፡፡ በሙያው ሌት ተቀን ሲያገለግልና የዕለት እንጀራውን ለፍቶ ለማግኘትም እድሜ ልኩን ሲታትር ኖሯል፡፡
ቶልስቶይ፤ በስፋት የሚታወቀው፤ ‹‹በአለም ላይ ከተጻፉት ረዥም ልቦለዶች ሁሉ ላቅ ያለ!›› ተብሎ ዘወትር በሚወደስለት ዋር ኤንድ ፒስ  (War and Peace) በተሰኘው ረዥም ልቦለዱ ነው፡፡ ያም ሆኖ፤ ቶልስቶይ፤ ከፍተኛ ዝና ያተረፉለትን ረዣዥም ልቦለዶቹንና ተውኔቶቹን ባይጽፍም ኖሮ፤ ስመ ገናና መሆኑ አይቀሬ ነበር - ባጫጭር ተረቶቹ፡፡
ተረቶቹን ልዩ የሚያደርጋቸው፤ ከመቶ አመታት በፊት በሩሲያ ውስጥ የነበረውን የጭሰኛውን ማህበረሰብ ህይወት ትክክለኛ ገፅታ ቁልጭ አድርገው በማሳየታቸው ነው፡፡ ታዲያ፤ በአጫጭር ታሪኮቹም ውስጥ ቶልስቶይ የሚተርክልን፤ ተደራሲውን በማዝናናት ለማስደመምና ለማስደነቅ ብቻ አይደለም፤አንዳች ፋይዳ ያለው መልዕክት ለማስተላለፍ እንጂ፡፡ እያንዳንዱ ታሪክ የተሸከመው ፍሬ ነገርም ቅልብጭ ብሎ በጥቂት ሀረጎች ይቋጠራል፡፡ የየመልእክቶቹ ጭብጥ ለሁላችንም ጠቃሚና የምንጊዜም  /important and everlasting/ መሆናቸው ደግሞ፤ሌላኛው ረቂቅ ውበቱ ነው፤ እፁብ ድንቅ የሥነ-ጽሑፍ ሰውነቱ ህያው አሻራ፡፡        
የፋሲካ በአል ማለዳ ነበር፡፡ በረዶው ገና ከዛፎቹ እቅፍ አልወረደም፡፡ ከየተዳፋቱ  እየተንደረደረ በያቅጣጫው በቀደደው ቦይ የሚንዠረዠረው ወራጅ ውኃ ፤ መንደሩን እያቆራረጠ ሾልኮ፤ በሰፊው አውራ መንገድ ላይ መገማሸሩን አላቆመም፡፡
ሁለት እምቡጥ ልጃገረዶች፤ወደየታዛቸው ሲያዘግሙ፣ በድንገት፣ ግራና ቀኝ በወሰን አጥር የተከለሉ ኩርማን እርሻ መሬቶች ከሚያዋስኑት ጠባብ መተላለፊያ ላይ ተገናኙ፡፡ አሰስ ገሰሱን አግተልትሎ ቁልቁል የሚንፎለፎለው ጎርፍ፤የማሳዎቹን ደረት እየገመሰ አልፎ፣ በአንድ ጎድጓዳ ስፍራ ውስጥ ተጠራቅሞ ኩሬ አበጅቷል፡፡
ከሁለቱ ልጆች አንዷ በዕድሜ አነስተኛ፣ ሌላኛዋ ተለቅ የምትል ናት፡፡ እናቶቻቸው ለአውደ አመቱ በገዙላቸው ልብሶች አሸብርቀዋል፡፡ ትንሽየዋ ሰማያዊ፤ ከፍ የምትለው ደግሞ ቢጫ ቀሚስ ለብሰው፣ ጸጉራቸውን በቀይ ጥብጣብ ሸብ አድርገዋል፡፡ ከቤተክርስቲያን እየተመለሱ ነበር፡፡ ገና እንደተያዩ፤የለበሱትን ቀሚስ በሩቁ በኩራት እያስተያዩ ተሳሳቁና ሳይነጋገሩ ተግባብተው ወዲያው ጨዋታ ጀመሩ፡፡ ሁለቱም፤ ውኃው ውስጥ ገብተው ማንቧቸር ነው የፈለጉት፡፡ ትንሿ ልጅ፤ ተጣድፋ እግሯን ወደ ኩሬው ስትሰድድ፤ ትልቅየዋ አስጠነቀቀቻት፡፡
‹‹ቆይ! እንዳትገቢ ማላሻ!›› አለች ‹‹ዋ! በኋላ እናትሽ ትገርፍሻለች! እኔ ጫማና ካልሲዬን አውልቄ ነው የምገባው፤አንቺም እንደኔ አውልቂ፡፡››
ጫማና ካልሲያቸውን አወለቁ፤ ቀሚሳቸውን ከጉልበታቸው በላይ ሰብስበው ይዘው፤ በውኃው ውስጥ እየረመረሙ፤ አንዳቸው ወደሌላቸው መጠጋጋት ጀመሩ፡፡ ማላሻ፤ ውኃው ከጉልበቷ ከፍ እያለ ሲመጣባት ‹‹ጥልቅ ሳይሆን አይቀርም አኩሊያ፤ፈራሁ!›› አለች፡፡
‹‹አይዞሽ!›› አለች ትልቋ ‹‹አትፍሪ፤ከዚህ በላይ ጥልቅ አይሆንም፡፡››
ተራርቀው ከነበረበት ሲቀራረቡ፤ አኩሊያ ‹‹አንቺ ማላሻ፤ውኃውን እንዳታንቦጫርቂ ተጠንቀቂ እሺ! ቀስ እያልሽ ተራመጂ›› አለች፡፡
አኩሊያ ንግግሯን ሳትጨርስ ግን፤ ማላሻ ከፍ አርጋ ያነሳችውን እግሯን ስታሳርፍ፤ ውኃውን በቅጡ ቸረፈሰችውና፤ ሽቅብ ጉኖ ሲዘንብ፤ አብላጫው አኩሊያ ልብስ ላይ ተረጨ፡፡ የሁለቱንም ፊት ገርፎ ያለፈው  ፍንጣቂ ባፍና አፍንጫቸው ጭምር ተሰረገበ፡፡ በጭቃ የላቆጠው የኩሬ ውኃ ዕድፍ አዲሱን ቀሚሷን ያበላሸባት አኩሊያ፤ በጣም ተናድዳ፤ ማላሻን ለመማታት እመር አለች፡፡ ማላሻ፤ አኩሊያ እንደማትለቅቃት ሲገባት፤ከሚደርስባት ብርቱ ኩርኩም ለማምለጥ፤ ቶሎ ብላ ከኩሬው ወጥታ፤ ወደ መኖሪያ ቤቷ አቅጣጫ ፈረጠጠች፡፡ አኩሊያ ማላሻን ስታባርር፤እናቷ ከቤት ወጣ ስትል፤ ግጥምጥም አሉ፡፡ እናትየው፤ የልጇ አዲስ ቀሚስ በጉድፍ ተዥጎርጉሮ ስታይ ጮኸችባት ‹‹አንቺ የማትረቢ ቆሻሻ ልጅ! ምናባሽ ስታደርጊ ነበር?!እ!››
‹‹ይቺ ማላሻ ናት አውቃ ያቆሸሸችብኝ!›› አለቻት ልጇ፡፡
 የአኩሊያ እናት፤ ማላሻን አሯሩጣ አንቃ ይዛ፤ደጋግማ ጀርባዋን በክንዷ ደቃቻት፡፡ ማላሻ፤እዬዬዋን ስታቀልጠው፤እሪታዋ በመንደሩ ዙሪያ አስተጋባ፡፡የልጇን የለቅሶ ድምፅ በሩቁ ሰምታ በራፏ ላይ ብቅ ያለችው የማላሻ እናት፤ፊት ለፊቷ ባስተዋለችው ነገር ፊጋ ሆና እየተንደረደረች ‹‹እንዴ! ምን አርጊ ብለሽ ነው ልጄን እንዲህ የምትደልቂያት አንቺ?!›› እያለች በጎረቤቷ ላይ ታንባርቅባት ጀመር፡፡ ‹‹እኮ ማነው አንቺን የኔን ልጅ ቀጪ ያረገሽ?!›› ባንዳፍታ የከረረ ንትርክ ገጠሙና፤ ሰፈሩ በሁለቱ እናቶች ፀብ ተቀወጠ፡፡ ባሎቻቸውም ከየቤታቸው ወጡ፡፡ አውራ መንገዱ በግርግርና ሁካታ ተናጠ፡፡ ሁሉም በየራሳቸው ጮክ ብለው ስለሚያወሩ፤መደማመጥ የሌለበት መጯጯህ ነገሰ፡፡ ለድብድብ መጋበዝ ሲጀምሩ ደግሞ የበለጠ ተተረማመሱ፡፡ አንዱ ሌላውን እየገፈተረ ጉሮሮ ለጉሮሮ ሊተናነቁ ደረሱ፡፡ አሮጊቷ የአኩሊያ አያት ብቻ ነበሩ ሁለቱንም ወገን ዝም ለማሰኘት መከራቸውን ያዩት፡፡
    ‹‹ምን እየሆናችሁ ነው ለመሆኑ ወዳጆቼ?አሁን እንዲህ መሆን ተገቢ ነው ?ያውም በዚህ ቀን! ፋሲካ የሰላምና የደስታ እንጂ የፀብ ጊዜ አለመሆኑ ጠፍቷችሁ ነው እውነት?››
  ማንም ጆሮ የሰጣቸው አልነበረም፡፡ ይልቁንስ እርስ በእርስ ሲጎሻሸሙ፤ለመገላገል መሀል የገቡትን ምስኪን አሮጊት ወዲያ አሽቀነጠሯቸው፡፡ በርግጥ፤የአሮጊቷ ግሳፄ፤እያጉረመረመ ለመቧቀስ የሚደገገውን የሁለት ጽንፍ ድንፋታ ማስከን ባይቻለውም፤አኩሊያና ማላሻን ግን የሁለቱም ተዋጊ ጦረኞች ሰልፍ አባልም ሆነ ደጀን ከመሆን ታድጓቸዋል፡፡ አዋቂዎቹ፤እንጥላቸው እስኪርገበገብ አፋቸውን እየከፈቱ መረን ለቅቀው ሲንቻቹ፤አኩሊያ፤አዲሱ ቀሚሷ ላይ የተመረጉትን የጭቃ ፍንጥቅጣቂዎች ፈግፍጋ እያስለቀቀች፤ተመልሳ ወደ ኩሬው ሄደች፡፡ ከዚያም፤ ሹሉን ስለታም ድንጋይ አነሳችና፤የኩሬውን ግርግዳ ካንድ በኩል እየነደለች፣ ውኃው፣ ከታቆረበት ጉድጓድ በሸነቆረችው ብስ በኩል አፈትልኮ ወደ አውራ መንገዱ እንዲንዠቀዠቅ አደረገችው፡፡ ማላሻም፤ወደ ኩሬው መጥታ አብራት ሆነችና፤ጫፉ የተሰነጠረ የእንጨት ቁራጭ ይዛ፤አኩሊያ የጀመረችውን፤የደለል ልስን ምርጊቱን ቦርቀቅ አድርጋ እየማሰች ረዳቻት፡፡ በሚያድጠው የፀቡ ስፍራ (የጦር አውድማ) ላይ፤ አዋቂዎቹ ክፉኛ በነገር ተነጃጅሰው፤እንደቆሰለ አውሬ አይናቸውን እያጉረጠረጡና ጥርሳቸውን እያፋጩ፤ በአጉል አፍ እላፊና በጉንጭ አልፋ ዝብዝብ ጉሮሯቸው እስኪደርቅ በከንቱ እየተዘላለፉ ተፋጥጠው ቆይተው፤ልክ ቡጢ መሰናዘር በጀመሩበት ቅጽበት፤የኩሬ ውኃው እንደ ደራሽ ጎርፍ እየተካለበ ደርሶ፤አሮጊቷ ለእርቅ ተማፅኗቸው  እንዲለመኗቸው እየተለማመጡ የቆሙበትን ቦታ ዳር ከዳር አለበሰው፡፡ሁለቱ ህጻናትም፤በወራጅ ውኃው እየተንከባለለ የሚወሰደውን ማላሻ የጣለችውን ቁራጭ እንጨት ለመያዝ ተከታትለው እየተሯሯጡ መቦረቅ ያዙ፡፡
  ‹‹ያዢው! ያዢው ማላሻ! ያዢው!›› ላንቃዋ እስኪላቀቅ እየተንከተከተች ትጮሀለች አኩሊያ፡፡ ማላሻ፤መናገር እስኪሳናት በሀሴት ፈንድቃ፤ ልቧ ውልቅ እስኪል በሳቅ ፍርስ ትላለች፡፡
 ሁለቱ ህጻናት፤ ቁራጩ እንጨት የሚያንገላታውን የወራጅ ውኃ ማዕበል እየሰነጠቀ፣ እየተገለባበጠና እየቀዘፈ  ሲንሳፈፍ ሲያዩት፤በደስታ ሲቃ ‹በክብር ተጋድሎ› በተጧጧፈው፣ ‹‹ጦር ሜዳ›› መሀል መሰስ አሉ፡፡ይህንን ሁሉ ጉድ በትዝብት የሚያስተውሉት አሮጊቷ፤ ወደ አዋቂዎቹ ዞር ብለው እንዲህ ሲሉ ተናገሩ…‹‹እሺ እዩ እስቲ ወገኖቼ፤አሁን እንግዲህ በራሳችሁ አታፍሩም? ሁላችሁም እንዲህ ያለ አታካራና ግብግብ የገጠማችሁት በእነዚህ ሁለት ህጻናት የተነሳ አልነበረም? ህጻናቱን ግን እዩዋቸው፤የተፈጠረውን ነገር ሁሉ እርስት አድርገው፤ ይኸው አብረው በሰላምና በደስታ እየተጫወቱ ነው፡፡ ልበ ንፁኃን እምቦቃቅላዎች! ደግሞ ከእናንት ከሁላችሁም እነርሱ ናቸው አዋቂዎች ፡፡››
አዋቂዎቹ ሁሉ፤ ወደ ህጻናቱ ተመልክተው በሀፍረት ኩም አሉ፡፡ በራሳቸውም ላይ እየሳቁ፣ አቀርቅረው ወደየቤታቸው ተመልሰው ገቡ፡፡
እነሆ፤በልቦናህ ካልተለወጥክ፤እንደ ህጻናትም ለመሆን ካልቻልክ፤በምንም መንገድ መንግሥተ ሰማይን አትወርሳትም፡፡

Published in ልብ-ወለድ

       ጸሐፊ ሌሊሳ ግርማ ሚያዝያ 8 ቀን 2006 ዓ.ም በታተመው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የተዋናይ ግሩም ኤርሚያስን ጉዳይ  መርምሮ ብይን የመስጠት ስልጣኑ ያለው ማህበረሰብ ሳይሆን ጥበብ ነው የሚል አቋሙን አስነብቦናል። በትንታኔው መሠረት ማንኛውም ከያኒ በስተመጨረሻ ጥበብን እስከወለደ ድረስ እንዳሻው ሊማግጥ ይቻለዋል። ማህበረሰብ እና ሕግ ጥልቅ የሚያደርጋቸው ነገር የለም። የአስተያየቱ አንድምታ ከያንያን ከብጤ የሰው ልጆች በሙሉ የላቁ በመሆናቸው እና / ወይም ፣ ኪነት ከሰው ልጅ ሙያዎች በሙሉ ልዕለ ከፍታን ስለተቆናጠጠች ማንም ቀና ብሎ ሊያይ አይገባውም ነው በአንድ በኩል። ይህ ካልሆነ ደግሞ ጥበብ እና ማህበረሰብ (ምናልባትም ተቧደነው ማህበረሰብን የመሠረቱት ግለሰቦች) የሚኖሩባቸው ንፍቀ ክበቦች የተለያዩ ናቸው ፤ ስለዚህም በአንዳቸው መስፈሪያ ሌላኛቸውን መለካት የተገባ አይደለም የሚል የንክኪ ትርጓሜ እናገኛለን። ይኹንና የሌሊሳን መከራከሪያዎች መያዣ መጨበጫዎች ማጣት ለመገንዘብ፣ ያንን ያህል ጠልቆ መጓዝ የሚያስፈልግ አይመስለኝም።
ገና በመጣጥፉ መግቢያ ላይ በሰይፉ መርኃ ትርኢት ላይ የቀረበውን እና የውዝግብ መነሻ የሆነውን ክፍል ያለመታደሙን ይናዘዝልናል።  “ባልከታተለውም ጉዳዩ ተብራርቶልኛል” ይለናል ይለጥቅና። ነገር ግን ሙሉ ጽሑፉን አንብበን ስንጨርስ የምንጋፈጠው ጥያቄ “በርግጥስ ጉዳዩ ተብራርቶለታል?” የሚል መሆኑ አልቀርም። ተብራርቶለት ቢሆንማ ኖሮ ወደ ውስጥ ጠልቆ የመተወን ስልት (ሜተድ አክቲንግ) ምንነትን ፣ ታሪክን እና ጀግኖችን “ለማስተዋወቅ” ብዙ አቅሙን ባላፈሰሰ ፥ ትምህርት ሊሰጠን ባልደከመ እና ባላደከመን ነበር። በእውቀት አጠር “እሪያነታችን” ከተማመነ በኋላ፣ “የእንቁውን” ትክክለኛ ዋጋ ገላልጦ ሊሳየንም ባልባተለ ነበር። በጉዳዩ ዙርያ ከተነሱ ወቀሳዎች አብዛኛው ያነጣጠሩት በመርኃ ትርኢቱ እና በአጋፋሪው ሰይፉ ፋንታሁን ላይ ነው። ለወቀሳዎቹ የቀረበው ኹነኛ መከራከሪያ በሚከተሉት ሁለት ጥያቄዎች ሊቀነበብ ይችላል፦ ያለ እድሜ እና ስሜታዊነት ገደብ ማንም በሚከታተለው የቴሌቪዥን ትርኢት ላይ የግሩም እጽ ወስዶ የመወነጋገር እውነተኛ ክስተት ስለምን ተቀንጭቦ ቀረበ? (ልብ ይባል— ቅንጭብ ትዕይንቱ ከፊልሙ ላይ የተወሰደ አይደለም። ምንም ዓይነት ኪነ ጥበባዊ ፋይዳም የለውም። ተዋናዩ ገፀ ባህርዩን “ለመሆን” ምን ያህል እንደተጓዘ ያሳያል ከተባለ እንኳ ፥ ይኼንን የማድረጊያ ሌሎች ብዙ ብልሃቶች መኖራቸው ሃቅ ነው።) ከምንም በላይ ደግሞ ትዕይንቱን የተከታሉ የስቱዲዮ ውስጥ ታዳሚዎች ለሚንገላወደው ግሩም (አሁንም ልብ ይባል— ለገፀ ባህርዩ ወይንም ለትወናው አይደለም) ስለምን የአድናቆት እስክስታ መውረድ ቃጣቸው?
ከዚህ የምንረዳው ጉዳዩ ከጥበብ ሕግጋት እና የነፃነት ፈቃድ ጋር ሳይሆን በየቤቱ ከሚያንኳኳው የቴሌቪዥን ትርኢት ገዥ ደንቦች ላይ መያያዙን ነው። መቼም በቀላል ፍረጃ “ማንም ሰው የመመልከት እና ያለመመልከት ነጻነት አለው” ተብሎ ሊገመደል አይችልም። ቴሌቪዥን ፊት ተጥደው በአባት ምርጫ መርኃ ትርኢቱን የሚጋቱ እምቦቃቅላዎች እና ታዳጊዎች “ነፃነት” አላቸው ተብለን በደረቁ እንደማንቀጠፍ እናምናለንና።
ጥበብ እና ማህበረሰብ (ከተነሳ አይቀር)
እጅግ ከማከብራቸው የፊልም ተዋንያን መካከል እመድበው የነበረው ፊሊፕ ሴይሞር ሆፍማን (ነፍስ ኄር) ሕይወት ሳይጠበቅ ማለፉን ተከትሎ ዝነኛው መጽሔት ዘ ኒውዮርከር ፥ “Is Method Acting Destroying Actors?” የሚል ርዕስ ያለው መጣጥፍ አትሞ ነበር። በመጣጥፉ ላይ ሌላኛው ተዋናይ ጄምስ ፍራንኮ እንዲህ ተጠቅሷል፦ “[የማርሎን] ብራንዶ ትወና የአሜሪካን አተዋወን ንጦ አብዮት አስነስቷል። ለዚህ ምክንያቱ ክዋኔ ላይ ያለ ስለማይመስል ነው። በዚያ አግባብ የሆነ ነገር ከመላበሱ ይልቅ ያንን ነገር መሆኑ ይበልጣል።”
“ሜተድ አክቲንግ” የሚባለውን ስያሜያዊ ሐረግ “የመሆን ትወና” ብሎ ወደ አማርኛ መመለስ አይስማማኝም። አንድ ተዋናይ ገጸ ባህርይውን ፍፁም ሆኖት ሲመደርክ ስናይ አተዋወኑን የምንገልፀው “እፁብ ድንቅ ትወና” እንጂ “ሜተድ አክቲንግ” ብለን አይደለም። “ሜተድ አክቲንግ” ወደ መሆን የመጓዣ መንገድ ነው። ሆኖ ለመተወን የሚረዳ ብልሃት ነው። ገፀ ባህርዩን ለመሆን በአነጋገር ዘዬ ፥ በተክለ አቋም ፥ እና በውስጣዊ ስሜት ራስን መከርከም ወይንም መለጠጥ ነው። እዚህ ላይ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ አለ፦ ተዋንያን ገጸባህርዮቻቸውን በስሜት ለመረዳት ምን ያህል መጓዝ አለባቸው? በሙያ ትጋት ወይም ቁርጠኛነት እና በጥንቃቄ አልባ ጀብደኛነት መካከል ቀጭን መስመር እንዳለች መዘንጋት የለበትም። ሥነ ልቦናዊ መጣመኑ በአካሉ ላይ የሚንፀባረቅ ሜካኒክን ገፀ ባህርይ “The Machinist” የተባለው ፊልም ላይ የተጫወተው ዌልሳዊው ተዋናይ ክርስትያን ቤል፣ የሰውነቱን ክብደት ሲቀንስ ፥ ልኩን በማለፉ “በቃህ” ያለ ኮስተር ያለ ትዕዛዝ ሊሰጠው እንደተገደደ ፥ አዘጋጁ ብራድ አንደርሰን የተናዘዘበትን ቃለ መጠይቅ ማዳመጤን አስታውሳለሁ። ጠርዝ መኖሩ የግድ ነው።
ከሌሊሳ መከራከሪያ ጋር በቀጥታ የሚገናኘው ሌላኛው መሠረታዊ ጥያቄ ግን ይህ ነው፦ ተዋንያን ገፀ ባህርዮቻቸውን ለመሆን ሲታትሩ ፥ የገፀ ባህርዩን አነጋገር እና አረማመድ ፥ አጻጻፍ ሳይቀር እንደሚኮርጁት ሁሉ ድርጊቱንስ መኮረጅ ይችላሉ? ያኔ ነው የግብረ ገብ እና የሕግ ጉዳይ የሚነሳው። አንድ ተዋናይ እፅ ተጠቃሚነት ምን እንደሚመስል ስሜቱን በተለያየ አቅጣጫ ፥ በተለያየ ስልት ፥ ከተለያየ ምንጭ ሊያውቀው ይችላል። ነገር ግን እጹን ተጠቅሞ ስሜቱን ለመረዳት ይችላል? ያ ማለት በሌላ ምንዛሬ ሕፃናት ደፋሪን ገፀ ባህርይ ስሜት ለመረዳት ሕፃናት መድፈር ለተዋንያን ሊፈቀድ ይችላል? ሚስቱን አንቆ የሚገድል ገጸ ባህርይን ለመጫወትስ ተዋናዩ አንድ የሚያንቀው ምስኪን ሊፈለግለት ነው? መልሶቹ ሲበዛ ግልፅ ናቸው። ኧረ በጭራሽ! ድርጊቶቻችን በበጐም በክፉም ያስጠይቁናል። ይህ ለጠቢብም ቢሆን አይቀየርም።
በርግጥ ሌሊሳ እንዳለው ማህበረሰብ በነሲቡ ስለተንጫጫ ወይንም በመንጋ ስላጓራ ሁሌም ልክ ነው ማለት አይደለም። ግን ደግሞ ከማህበረሰብ ማፈንገጥም በራሱ ግለሰባዊ የምግባር ልዕልና አይደለም። ፍሬ ነገሩ ያለው ከድርጊቱ ግብረ ገባዊ እና አመክንዮኣዊ ልክነት ላይ ነው። ለምሳሌ የግሩምን ድርጊት ለማጽደቅ ሌሊሳ የተጠቀመበት አንደኛው መከራከሪያ በግርድፉ “ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ በእጽ ሱስ ናውዟል። ተዋናዩ ይኼንን በማሳየቱ ልንወቅሰው አይገባም” ይላል። ሱሰኝነትን ማሳየቱ ተዋናዩን ወይንም ሌላ ማንኛውንም ከያኒ አያስወነጅልም። ማህበረሰብን ማነጽ ያለ ማነጽ እዚህ ውስጥ ሳይገባ ፥ ጉዳዩ አንድ የሰው ልጅ ህልውና እውነታ ስለሆነ በጥበብ ከመዳሰስ እንዳያመልጥ ያደርገዋል። ነገር ግን ሱሰኝነትን (ሱስ ላይ ባይደርስ እንኳ እጽ መጠቀምን) የሚያሳየን ሱሰኛ በመሆን (እጽ በመጠቀም) ሊሆን አይገባውም። ያ አመክንዮኣዊ መጣረስ ወይንም ሁለት ዓይነት ምዘና እንዲኖረን ያደርጋል። እጽ ተጠቃሚነትን ከተጸየፍን ፥ ተዋናዩም እፅ መጠቀሙን እንጠላለን። አለቀ። ነገር ግን ይኼኛው የሌሊሳ መሟገቻ ከዚህም የባሰ አስደንጋጭ እይታ ይዟል። የመረጃ መረብ ልቅ መሆን ሕዝቡን እንዳሻው የጭካኔ ትዕይንት የሚበዛባቸው ፊልሞችን እንዲታደም ክፍት ትቶታል ፤ ስለዚህ የግሩም በእጽ ሲንገላወድ በአደባባይ መሰጣት ችግር የለውም ዓይነት ነገር ይለናል። ይህ ድርጊት በራሱ እንጂ መገምገም ያለበት ከሌላ ኩነቶች ጋር ተናብቦ የማህበረሰባዊ ግብዝነት ማሳበቂያ ሊሆን እንደማይገባው ሊያስተውል የፈቀደ አይመስልም። ትክክል ነው ግብዝነታችን ያሳፍራል። ያ ግን ግሩምን ትክክል አያደርገውም።
እነዚህን እና የመሳሰሉ መውሸልሸሎችን ነቅሰን ካየን በኋላ፣ ‘ተከባሪው ሌሊሳ እንደምን እንደዚህ ያለ ቱማታ መጣጥፍ ለመጻፍ ተነሳሳ?’ ብለን ስለ መግፍኤው መላ መምታት ይቀረናል። እኔ ሦስት ብቻ አማራጭ ገፊ ምክንያቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ ይታየኛል። አንድ ለግሩም ኤርሚያስ የተለየ መውደድ ስላለው ፍቅሩ ዓይኑ ላይ ሞራ ለድፎበታል። ሁለት ጅረቱን በተቃራኒ አቅጣጫ በዋና ለመጋፈጥ ሲል ብቻ ብዕሩን አሹሏል። ሦስት ጉዳዩን “the so called ማህበረሰቡን የሚያንጹ አስተማሪ ጥበቦች” የሚቀሰቅሱበትን ብሽቀት ለማራገፍ እንደ አጋጣሚ ተጠቅሞበታል ወይንም በአምልኮተ ጥበብ አቅል ስቶ ፥ ነገድ ለይቶ ጦር መምዘዝ አሰኝቶታል። ከሦስቱ አማራጭ መላ ምቶች መካከል ቀዳሚው ብዙም ውሃ የሚያነሳ መስሎ  ስለማይታየኝ እንዲሁ ከማለፍ የበለጠ ትኩረት አልሰጠውም። ሁለተኛው መላ ምትም ያንን ያህል አላሳመነኝም።
ወደ ሦስተኛው እና በይሆናል ሚዛን ከፍ ያለ ድርሻ ያነሳብኝን መላ ምት አስመልክቼ አንዲት ቀጭን የሙግት ክር ለመምዘዝ ያህል እንዲህ እላለሁ። ለእኔ ጥበብ ሰባካም ባይሆን ግብ አላት። ማህበረሰብን ማነጽ እና ማረቅ የሻተ ጠቢብ ከተነሳ እሰየው። ቁልፉ ነገር ዒላማው ሳይሆን መንገዱ ነው። ምክንያቱ ሳይሆን አከዋወኑ ነው። ማህበረሰብን ማነጽ ስለሻተ ብቻ ለእንቶ ፈንቶነቱ አታሞ አንመታም። ይኹንና ያለ ምንም ግብ ለመጠበብ ሲባል ብቻ አይጠበብም። ግጥም ለመፃፍ ብቻ ግጥም አይጻፍም። ፋይዳ አለው። ግቡ አንዳች መልዕክት ማስተላለፍ ላይ ተለጉሟል ማለት አይቻልም። ውበት ሊሆን ይችላል። የህልውናን ቅጣምባር መበርበር ፥ ጓዳ ጐድጓዳውን መፈተሽ ሊሆንም ይችላል። ከዚህም ባሻገር ጥበብ ኦና ውስጥ አትኖርም።
ሰዋዊ ናት። ከሰው የማንነት ቅንጣቶች መካከል አንዷ ናት። ለዚያም ነው አልፎ አልፎ የማየው አምልኮተ ጥበብ (fetishism of art) የሚጐራብጠኝ። በቅርቡ የሥነ ጽሑፍ ኅልዮት አርቃቂው እና ፈላስፋው ቴሪ ኤግልተን “Culture and the Death of God” የተሰኘ ድርሳን አሳትመዋል። ሰውየው ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪሽ ኒቸ “እግዚሃር መሞቱን” ለዓለም “ካረዳ” በኋላ በዓለማችን ባህል እና ስልጣኔ ላይ ምን እንደተከሰተ ያጠይቃሉ። የተለወጠው ነገር —— ይላሉ ኤግልተን — በእግዚሃር ስፍራ ሌሎች መተካታቸው ነው። ቦታውን ተክተው በአምልኮ ግዝፈት የሚታዩ ብሎም የሁሉም ተከታይ እርምጃዎች ማጣቀሻ ነጥብ የሆኑት ነገሮች አመክንዮ ፣ አገር ፣ ተፈጥሮ ፣ ፣ ሰብዓዊነት ፣ ስነ ልቦና እና አዎ ጥበብ የመሳሰሉት ናቸው።
ሌሊሳ ለዓመታት በሚያነሳቸው እሳቦቶች እና እሳቦቶቹን በሚመሰርትበት ቅጥ ስማረክ ቆይቻለሁ። አሁንም ምርኮው ነኝ። ነገር ግን አልፎ አልፎ እንዲህ በቅርታ ማልጐምጐሜ አልቀረም።

Published in ጥበብ
Saturday, 26 April 2014 13:02

የግጥም ጥግ

ዝም ብንል ብናደባ
ዘመን ስንቱን አሸክሞን፤
የጅልነት እኮ አይደለም
እንድንቻቻል ነው ገብቶን፡፡
 ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን
ቅልስልሱ ይሁዳ
ይሁዳማ ቅልስልስ ነው
አቅፎና ደግፎ
ክርስቶስን ሰጠ
ለሞት አሳልፎ፤
የኛ ዘመን ሰው ግን
ሰቅሏችሁ ሲያበቃ
በፈገግታ ክቦ፤
አቅፎ ይስማችኋል
አይኑን በጨው አጥቦ፡፡
                                       አማኑኤል  መሀሪ
ስሙነኛ ስንኝ
የህዝቦች ልቦና
በታሪክ አንደበት፤
‹‹ንጉሥ ነህ!!›› ባለ አፉ
የሆሳዕና ለት፤
‹‹ስቀለው!!!›› ይልሀል
ውሎ አድሮ እንደ ዘበት፡፡
                                        ፈለቀ  አበበ                           


Published in የግጥም ጥግ

      የ25 ዓመቱ ሳላሀዲን ሰኢድ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃዎችን በአዳዲስ ክብረወሰኖች እያሻሸለ  እድገቱን በመቀጠል ላይ ነው፡፡ ከ3 አመት በፊት ለግብፁ ፕሪሚዬር ሊግ  ክለብ ዋዲ ዳግላ ለመጫወት በተከፈለበት 275ሺ ዶላር የዝውውር ሂሳብ አዲስ ታሪክ  ያስመዘገበው  ሳላሀዲን ሰኢድ ሰሞኑን  ደግሞ  ወደ ሌላው የግብፅ ክለብ አልአሃሊ  በመዛወር በወር 30 ሺ ዶላር እየተከፈለው ለመጫወት ተስማምቶ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ አዲስ ክብረወሰን አስፅፏል ፡፡ ሳላሃዲን በአልአሃሊ በሚቀጥሉት 3 ዓመታት ሲጫወት ከ500ሺ ዶላር በላይ ያገኛል በሚል የዘገበው ሱፕር ስፖርት ነው፡፡
 በግብፁ ክለብ ዋዲ ደጋላ ዘንድሮ 11 የሊግ ግጥሚያዎችን ያደረገው እና በ9 ጨዋታዎች ቋሚ ተሰላፊ የነበረው ሳላሃዲን 6 አስደናቂ ጎሎችን ከመረብ ማዋሃዱ ትኩረት ውስጥ ከቶታል፡፡ ከሳምንት በፊት ሳላሃዲን በዋዲ ደጋላ  የሚቆይበት የኮንትራት ውሉ ዘንድሮ ማብቃቱን የሚያወሱ ዘገባዎች  መውጣት የጀመሩ ሲሆን በክለቡ ቆይታውን እንዲያራዝም ግፊት ቢደረግበትም የዝውውር ህገ ደንብን ጠብቆ መልቀቁ እንደማይቀርና ወደ ሃያላኖቹ የግብፅ ክለቦች ዛማሌክ ወይም አልአሃሊ ሊዛወር እየተደራደረ  ነው የሚሉ መረጃዎች ተናፍሰው  ነበር፡፡ ከወራት  በፊት ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ክለብ ካይዘር ቺፍ ተጨዋቹን ለማስፈረም ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጉ ተወስቷል፡፡
ቀይ ሰይጣኖች የሚባለው  የግብፁ ክለብ አልአሃሊ  ባለፈው የውድድር ዘመን የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን  ሳላሃዲን ሰኢድን ዘንድሮ እየተሳተፈበት በሚገኘው  የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ማሰለፍ አይችልም፡፡
ሳላሃዲን ሰኢድ በኢትዮጵያ ብሄራዊ  ቡድን የአጥቂ መስመር ተጨዋችነት ባለፉት 2 ዓመት ከሰባት ወራት 20 ጨዋታዎችን አድርጎ 12 ጎሎችን  በስሙ እንዳስመዘገበ ይታወቃል፡፡ በካፍ ዓመታዊ ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋች ምርጫ በመላው ዓለም ከሚጫወቱ አፍሪካዊ ፕሮፌሽናሎች በእጩነት ከቀረቡት  25 ተጨዋቾች አንዱ የነበረው ሳላዲን ሰኢድ በትራንስፈር ማርኬት የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ 300ሺ ዩሮ ነው፡፡

ከ3 ወራት በላይ የፈጀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ቅጥር ሰሞኑን በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ እና በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ መካከል በተፈረመው የውል ስምምነት ተቋጭቷል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ  የቅጥሩ ሂደት የዘገየው ውጤታማ  አሰልጣኝ ለመቅጠር በተከተልነው ጥንቃቄ የተሞላበት አሰራር  ነው ብለዋል፡፡ የፊታችን ሀሙስ በይፋ ስራቸውን የሚጀምሩት ዋና አሠልጣኙ ማርያኖ ባሬቶ ከማክሰኞው የፊርማ ስነስርዓት በኋላ ባለቤታቸውንና አንድ ልጃቸውን ወደ አዲስ አበባ  ይዞ ለመምጣት  ወደ አገራቸው ተጉዘዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በአሰልጣኙ ቅጥር ምንም ደላላ እንዳልገባበት የገለፀ ሲሆን የፊርማም እንዳልተከፈለ አመልክቷል፡፡
በባህርያቸው ቀጥተኛ እና ግልፅ ሰው መሆናቸውን፤ ውሸት እና አሉባልታ እንደማይወዱ ለስፖርት አድማስ የተናገሩት ማርያኖ ባሬቶ፤ በሙያቸው በታታሪነት በማገልገል ስኬታማ መሆን ዋና ትኩረቴ  ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሃላፊነት ለመስራት የወሰንኩት ጉልህ ለውጥ ለመፍጠር የምችልባቸው እድሎች በመመልከቴ ነው ካሉ በኋላ፤  በእግር ኳሱ ዙርያ ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በወጣት እና ታዳጊ ተጨዋቾች በትኩረት ለመስራት   ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው እንዳነሳሳቸውና  ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ተጨዋቾችን በፕሮፌሽናል ደረጃ  እስከ አውሮፓ ማሳደግ እንደትልቅ ሙያዊ ስኬት   የሚቆጠር መሆኑን   ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በገቡ በማግስታቸው አዲሱ የስራ ሃላፊነት ትልቅ ክብር መሆኑን ተገንዝቤያለሁ ያሉት ማርያኖ አዲስ አበባን ዞር ዞር ብለው በጎበኙበት ወቅት የከተማዋ ሰላማዊነት ማርኮኛል ብለው፤ የህዝቡ አቀባበል  ደስ እንዳላቸውና በተለይ እግር ኳስ የሚወደድበት አገር ለመስራት ጉጉት ተፈጥሮብኛል ብለዋል፡፡የኢትዮጵያ እግር ኳስ በማይናወፅ መሰረት ላይ ተገንብቶ በእድገት አቅጣጫ እንዲጓዝ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ እድሉን በማግኘታቸው ተደስቻለሁ ያሉት ዋና አሰልጣኙ፤ ከሁሉም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ቅን የሆነ ድጋፍ እንደማገኝ አምናለሁ  ብለዋል፡፡  
በ2ዓመት 10 ሚሊዮን  ብር የሚስወጣው ውል
በቅጥር ሂደቱ የመጨረሻ እጩዎች ከነበሩት አሰልጣኞች መካከል በአንደኛ ደረጃ  ታስበው ከነበሩት  ሰርቢያዊው ጎራን ስቴፋኖቪች ያልተሳካ ድርድር በኋላ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከሌሎቹ የመጨረሻ እጩዎች ከፖርቱጋላዊያኑ ማርያኖ ባሬቶ እና ዞራን ፍሊፖቪች እንዲሁም ከስዊድናዊው ላርስ ኦሎፍ ማትሰን ግንኙነት ያደረገው ወዲያውኑ ነበር፡፡  በመጨረሻም የእግር በተለያዩ ሃሳቦች በመቀራረቡ አሰልጣኙ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ጋበዘ፡፡ ባለፈው ሰኞ እና ማክሰኞ የመጨረሻው ድርድር በማከናወን ከስምምነት ላይ  ደረሰ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከማርያኖ ባሬቶ ጋር ባደረገው ድርድር ዋናው ትኩረት የደሞዝ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን በተመለከተ ነበር፡፡ በ2 አመት  ኮንትራት ቅጥር ለማርያኖ ባሬቶ 18 ሺ ዶላር ወርሃዊ የተጣራ ደሞዝ ለመክፈል የተስማማው  ፌደሬሽኑ የአሰልጣኙን የመኖሪያ ቤት፣ ተሽከርካሪና ነዳጅ የመሳሰሉት ጥቅማ ጥቅሞች  ይሸፈንላቸዋል፡፡ አቶ ጁነዲን ባሻ   እንደተናገሩት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ  የዋና አሰልጣኙን ደሞዝ እና ሌሎች ወጭዎች ቢያንስ ለ3 ወራት ከካዝናው ለመክፈል ያስባል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን መንግስት፤ ስፖንሰሮች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሰጡትን ድጋፍ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ማርያኖ ባሬቶና እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የገቡትን ውል  ለማፍረስ ከፈለጉ ከ3 ወራት በፊት ማሳወቅ አለባቸው ተብሏል፡፡ ማርያኖ ባሬቶ ከብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሃላፊነታቸው ጎን ለጎን በሚያከናውኗቸው ተግባራት ዙርያ ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በውሉ መሰረት ማርያኖ ባሬቶ  በኢትዮጵያ እግር ኳስ የአሰለጣጠን ስርዓት ውስጥ ለውጥ እንዲፈጥሩ ተፈልጓል፡፡ መሰረታዊ እና ዘላቂ ውጤት የሚገኝበትን አሰራር በመዘርጋት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም ተጠይቋል፡፡ በተለይ ደግሞ በታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በማከናወን በዘላቂ መሰረት ላይ ብሄራዊ ቡድኑን እንዲገነቡ መመርያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ከላይ በተዘረዘሩት አቅጣጫዎች  ከአገሪቱ የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ጋር ተቀራርበው የሚሰሩ ሲሆን ከየክለቡ  አሰልጣኞች፤ አመራሮች እና  ከተጨዋቾቻቸው ጋር ወጥ በሆነ ግንኙነት እንደሚንቀሳቀሱ ፤ ልምዳቸውን በማጋራት እንደሚሰሩና ኢትዮጵያዊ ተጨዋቾች በፕሮፌሽናል  ደረጃ ስኬት እንዲኖራቸው መሰረታዊ አቅጣጫዎች እንደሚነድፉም ይጠበቃል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ  በብሄራዊ ቡድኑ ከኢትዮጵያዊ ረዳት አሰልጣኞች ጋር ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውም ሲታወቅ አስፈላጊው የእውቀት እና የክህሎት ሽግግር ለመፍጠር  እንደታሰበ ተገልጿል፡፡
ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ እስከ ግማሽ ፍፃሜ መድረስ ከማርያኖ ባሬቶ
እስከ 12 ሚሊዮን ብር በጀት ከፌደሬሽን
ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2015 እኤአ ለሚደረገው የሞሮኮው 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸው ይጠበቃል ያሉት የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ሲሆኑ፤ በአፍሪካ ዋንጫው ገብቶ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ከምድብ ፉክክር ባሻገር ለግማሽ ፍፃሜ በመድረስ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ከ10 ወራት በኋላ ሞሮኮ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፉ 15 ቡድኖችን ለመለየት ለሚካሄደው ማጣርያ የምድብ ድልድሉ ነገ በካይሮ ከተማ ይወጣል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለምድብ ድልድሉ  በቀጥታ የደረሱትን 21 አገራት እና  በቅድመ ማጣርያ ካለፉት አገራት ጋር በመቀላቀል ከእጣ አወጣጡ በፊት በአራት ማሰሮዎች በመመደብ  አሳውቋል፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ያለቅድመ ማጣርያ ለምድብ ማጣርያ ውድድር  የበቃችው ኢትዮጵያ በማሰሮ 3  ከቤኒን፣ ከአንጎላ፣ ከኒጀር፣ ከዚምባቡዌ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከማላዊ፣ ከብሩንዲ፣ ከላይቤርያ እና ከሱዳን ጋር ትሆናለች፡፡ በማሰሮ 1 የሚገኙት ናይጄርያ፣ ቡርኪናፋሶ፣  ኮትዲቯር፣  ቶጎ፣  ማሊ፣  ደቡብ አፍሪካ፣  ኬፕቨርዴ ፣  ዲሪ ኮንጎ፣  ዛምቢያ፣  ቱኒዚያ እና ጋና ፤በማሰሮ ሁለት ግብፅ፣  ሊቢያ፣  አልጄርያ፣  ሴኔጋል፣  ካሜሮን ፣ ጊኒ፣  ሴራልዮን፣  ጋቦን፣  ኡጋንዳ ፣ ኮንጎ ኪንሻ እና ማዕከላዊ አፍሪካ፤ እንዲሁም በማሰሮ 4 ቅድመ ማጣርያ ያደረጉት አገሮች ተመድበዋል፡፡ ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  የሚደረገው  ምድብ ማጣርያ  ከ5 ወራት በኋላ ሲጀመር የምድብ ማጣርያው  28 ብሄራዊ ቡድኖች በሰባት ምድቦች ተደልድለው በሁለት ወራት ውስጥ እያንዳንዳቸው 6 የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በማድረግ የማለፍ እድላቸውን ይወስናሉ፡፡ በማጣርያው ሂደት ከሰባቱ ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የሚያገኙት 14 ቡድኖች በቀጥታ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ፤ ከሁሉም ምድቦች በምርጥ ሶስተኛነት የሚያልፈው 15ኛው ቡድን ይሆናል፡፡ ሞሮኮ በአስተናጋጅነቷ 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድን ሆና በቀጥታ ታልፋለች፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2015 እኤአ ለሚደረገው አፍሪካ ዋንጫ ለመብቃት ቢያንስ እስከ 12 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚያስፈልገው ለመገመት ተችሏል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለብሄራዊ ቡድኑ ይህን በጀት ለሟሟላት ከቴሌቭዥን ስርጭት መብት፤ ከስታድዬም ትኬት ሽያጭ፤ ከተለያዩ የስፖርት ቁሳቁሶች ሽያጭ እና ከስፖንሰርሺፕ ድጋፎች ከሚያገኛቸው ገቢዎች ባሻገር  ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፎችን ከመንግስት እና ከሌሎቹ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡
ለታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾችና ውድድራቸው አበረታች  ትኩረት በፌደሬሽን
በአውሮፓ ደረጃ ልምድ የመቅሰም ፕሮጀክት በማርያኖ ባሬቶ
ብሄራዊ ቡድን ብቻውን መቆም የለበትም ያሉት የእግር ኳስ  ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ፤ ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ከክለቦች፤ ከሀ-17 እና ሀ-20 ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡ ባለፉት 2 ዓመታት በዋናው ብሄራዊ ቡድን ከተፈጠረው መነቃቃት በኋላ ስልጣኑን ከያዘ መንፈቅ  እንኳን ያልሆነው የእግር ኳስ ፈደሬሽን ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ በታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ላይ መሥራት፣  እነሱንም ለፕሮፌሽናል ደረጃ ማብቃት እና ተተኪ ማድረግ ያስፈልጋል በሚል አቅጣጫ በመስራት ጉልህ እርምጃዎችን እንደወሰደ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረትም ከ20 ዓመት በታች እና ከ17 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ብሔራዊ ቡድኖች በብሄራዊ ፌደሬሽኑ የተዋቀሩ ሲሆን በክለቦች ከ17 ዓመት በታች ውድድር በተቃና ሂደት ላይ ነው፡፡
በታዳጊ እና ወጣት ብሄራዊ ቡድኖች ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች እንዲሰሩም ተደርጓል፡፡ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሠልጣኝ ወንድማገኝ ከበደ በመሰልጠን ላይ የሚገኝ ሲሆን ወደ አፍሪካ ወጣቶች እግር ኳስ ዋንጫ እያደረገ ያለውን ማጣርያ ጨዋታ ወደ ሲሸልስ አምርቶ 2ለ0 አሸንፎ መልካም አጀማመር አሳይቷል፡፡  
ሰሞኑን ደግሞ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ   ከ17 ዓመት በታች ላለው ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን የዋና አሠልጣኝ ቅጥር ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ለሃላፊነቱ የተመረጡት የቀድሞው የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር  ኢንስትራክተር ዮሐንስ ሳሕሌ ናቸው፡፡  ማርያኖ ባሬቶ በተለይ በወጣቶች ላይ በመስራት እግር ኳሱ ለእድገት በሚያመች መሰረት ላይ እንዲቀመጥ እና እንዲሻሻል ፍላጎት አላቸው፡፡  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት ከመምራት ጎን ለጎን የታዳጊ እና ወጣት ቡድኖችን በመከታተል፤ በየጊዜው የሚመረጡ ወጣቶችን ወደ አውሮፓ ትልልቅ ክለቦች የሚወስዳቸውን አቅጣጫዎች እንደሚዘረጉ ቃል የገቡት ዋና አሰልጣኙ ፤  ከፖርቱጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን ፕሬዝዳንት ጋር በስልክ ተነጋግረው የክለቡ አካዳሚ ለኢትዮጵያን እግር ኳስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ  መሆናቸውን ገልፀውልኛል ብለዋል፡፡ በዚህ እቅዳቸው መሰረት የተመረጡ የኢትዮጵያ ወጣት ተጨዋቾችን ወደ ስፖርቲንግ ሊዝበን አካዳሚ በየጊዜው በመላክ 1 ወር እና ከዚያም በላይ ካምፕ ገብተው ስልጠና እንዲያገኙ እና ልምድ እንዲቀስሙ ለማድረግ እሞክራለሁ ይላሉ፡፡ በዓለም እግር ኳስ ከሚታወቁ ምርጥ የእግር ኳስ አካዳሚዎች አንዱ ከሆነው የፖርቱጋሉ ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን አካዳሚ መውጣታቸውን ማርያኖ ባሬቶ  በማስታወስ አካዳሚው ታላላቆቹን የፖርቱጋል ተጨዋቾች እነ ልዊስ ፊጎ፤ ሲሞን ሳብሮሳ፤ ሊውስ ናኒ እና ክርስትያኖ ሮናልዶን ያፈራ ነው ፡፡ በአሰልጣኝነት በሰራሁባቸው አገራት ለወጣት ተጨዋቾች የፕሮፌሽናል እድገት አስተዋፅኦ የነበራቸውን ስራዎች በትኩረት አከናውኛለሁ ያሉት ማርያኖ ባሬቶ፤ በጋና ቆይታቸው ወቅት በአሁኑ ወቅት አለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን እነ ማይክል ኤሲዬን፤ አሳሞሃ ጊያን እና ሱሊ ሙንታሪን ወደ ዋናው ቡድን በመቀላቀል ስኬታማ ማድረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል በቆይታቸው ኢትዮጵያዊ እግር ኳስ አሰልጣኞች የሙያ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበትን ሁኔታ ፈጥረው ፤ በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ተወስደው ወቅታዊ የስልጠና እውቀት እንዲቀስሙና የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
ማርያኖ ባሬቶ በአፍሪካ ባላቸው ልምድ ተማምነዋል፤ ስለጋና ታሪካቸውም ይናገራሉ
የ57 ዓመቱ ማርያኖ ባሬቶ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የፕሮፌሽናል አሰልጣኝነት ፍቃድ አላቸው፡፡ እግር ኳስ በከፍተኛ  ደረጃ ተወዳጅ በሆነባቸው ፖርቱጋል፤ ራሽያ እና ጋና ላለፉት 10 ዓመታት በቆዩበት በስራ ዘመናቸው በብሄራዊ ቡድንና በክለብ ደረጃ በዋና እና በረዳት አሰልጣኝነት ከፍተኛ ልምድ አካብተዋል፡፡ የአካል ብቃት ኤክስፐርት ሆነውም አገልገለዋል፡፡  
ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ በአፍሪካ ባላቸው ልምድ ከፍተኛ መተማመን እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በወጣትነታቸው በሞዛምቢክ ለ7 ዓመታት  መኖራቸውን እየገለፁ ፤ የጋና ብሄራዊ ቡድኑን በማሰልጠን  በኦሎምፒክ መድረክ የነበራቸውን ተሳትፎ እና ከዚያም ቡድኑን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ እንዲያልፍ ማድረጋቸውን እንዲሁም  በአንጎላም ክለብ በመስራት በቂ ልምድ እንዳላቸው ጠቃቅሰው  በስፖርቱ ዙርያ  ብዙ ጓደኞቻቸው አፍሪካውያን በመሆናቸው  የአፍሪካን እግር ኳስ ጠንቅቀዉ እንደሚያዉቁ ይናገራሉ፡፡
ማሪያኖ ባሬቶ  የጋናን ብሔራዊ ቡድን በመምራት ያሳለፉትን የ9 ወራት ቆይታቸውን ስኬታማነት እና አወዛጋቢነትም በተመለከተ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከ10 አመት በፊት የጋናን ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን በተረከቡበት ወቅት በማጣርያ ውድድር ዛምቢያ፤ ደቡብ አፍሪካ እና  አልጄርያን አሸንፈው በግሪክ አቴንስ ተዘጋጅቶ ለነበረው ኦሎምፒክ ማለፋቸውን ሲያስታውሱ ከኮሎምቢያ ጋር 2 እኩል እንዲሁም ፓራጓይን 2ለ1 በመርታት ከምድባቸው ቢያልፉም ያኔ በጁቬንትስ ይጫወት የነበረው ስቴፈን አፒያህ  በአምበልነት የሚመራው ቡድናቸው በጥሎ ማለፍ በጃፓን 1ለ0 ተሸንፈ ብለዋል፡፡
 ከኦሎምፒክ በኋላ ደግሞ የጋናን ብሔራዊ ቡድን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በ2006 እኤአ ጀርመን ላዘጋጀችው ለዓለም ዋንጫ አብቅተዋል፡፡ በአጠቃላይ ማርያኖ ባሬቶ በጋና ቆይታቸው በማጣርያ፤ በዋና ውድድሮች እና በአቋም መፈተሻ 33 ያህል ጨዋታዎችን አድርገው ሽንፈት ያጋጠማቸው በአንድ ጨዋታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር ለሁለት ዓመታት የተፈራረሙትን ኮንትራት ስራዬን ለማከናወን የጋና እግር ኳስ ፌደሬሽን በቂ ትብብር አላደረገልኝም የሚል ምክንያት አቅርበው  በገዛ ፈቃዳቸው ለቅቀዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የጋና እግር ኳስ ፌደሬሽን  ማርያኖ ባሬቶን ከስራቸው ስለመልቀቃቸው አስፋላጊውን ማስጠንቀቂያ ከ3 ወራት በፊት አላሳወቁኝም በሚል ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር  ፊፋ ክስ አቅርቦ 85 ሺ ዶላር የገንዘብ ቅጣት  በአንድ ወር እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡ ከጋና ጋር የነበረኝ ቆይታ ሲቋረጥ የተላለፈብኝን ቅጣት ከኪሴ ከፍዬ ነበር ያሉት ማርያኖ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በሚኖረኝ ቆይታ   የማይመች አሠራር ካለ ለቅቆ የመሄድ መብቴ የተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

           በሚያዝያ ወር 2006 ዓ.ም መግቢያ ላይ በመዲናችን አንድ መጽሐፍ ለምረቃ በቅቶ ነበር፡፡ ቦታው በብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍ አዳራሽ ውስጥ ነበር፡፡  የመጽሐፉ ርዕስ “ኢትዮ-ኤርትራ የቀን ግርዶሽ” የሚል ነው፡፡ በመጽሐፉ ምረቃ ላይ ለመገኘት የቻልኩት በአንድ ጓደኛዬ ጥቆማ መሰረት ነበር፡፡ የመጽሐፉ ጸሐፊ ተስፉ (ኢትዮጵያ) አልታሰብ ማንነት፤ በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ኤርትራ ተወልዶ ያደገ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በስሙ መካከል የገባው “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም የእናቱ ነው፡፡ “ለምን የእናትህን ስም ከአባትህ አስቀደምክ?” ሲባል “የሴት ልጅ መባል በሀገራችን እንደ ስድብ ስለሚታይ በእናት መጠራት ውርደት ሳይሆን ክብር መሆኑን ለማሳየት ነው” ብሏል፡፡  
ጸሐፊው ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በ1983 ዓ.ም ሲሆን፤ ከኤርትራ አወጣጡን በግፍ እንደነበር በመጽሐፉ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ፀሐፊው በወቅቱ በሻእብያ መንግስት ካደገበት ከአስመራ በግዳጅ መውጣቱን ይናገራል፡፡ ነገር ግን ይህን የግፍ ድርጊት የፈፀመው የሻእብያ መንግስት እንጂ የኤርትራ ሕዝብ አለመሆኑን በመጽሐፉ ላይ ምስክርነቱን አስቀምጧል፡፡ ከዚህም ባለፈ የማባረሩን ድርጊት የፈጸሙት የሻእብያ መሪዎች፣ ዛሬ በሰሩት ስህተት ተምረውበት ይሆናል በማለት ይቅር ልንላቸው ይገባል፤ በማለት ስለ ይቅር ባይነትና ቂምን መያዝ አስፈላጊ አለመሆን በመፅሀፉ ይነግረናል፡፡ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የነበረው ጸሐፊው፣ ድርጊቱን የፈፀሙት በጣት የሚቆጠሩ የሻእብያ መሪዎች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከኤርትራ እንዴት እንደተባረሩ ለማናውቀው ዜጎች እውነታውን ለማሳየትና በኤርትራ ሕዝብ ላይ ምንም አይነት ቂም እንዳንይዝ በማስረጃ እያጣቀሰ፣ በጉዳዩ ላይ እውነታውን እንድናውቅና ከኤርትራ ህዝብ ጋር በፍቅር መኖር እንደሚገባን በስፋት ይነግረናል፡፡   
ከዚህ ቀደም የሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት የደም፣ የስጋ፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የልማድና የሥነ-ልቦና ትስስር እንዴት እንደነበረ ኤርትራ በኖረባቸው ሃያ ዓመታት ያየውን፤የሰማውንና ያነበበውን እውነታ በመጽሐፉ አስቀምጧል፡፡ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ስለ ሁለቱ ሕዝቦች ፍቅርና አንድነት የሚተርክልን መጽሃፉ፤ ወደፊት ይህን የሁለቱ ህዝቦች ፍቅርና አንድነት እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻል መፍትሄዎችን ይጠቁማል፡፡
ዛሬ ግን በሀገራችን ያሉ የክልል ባለስልጣናት የሚሰሩትን ስራ ስንመለከት በግልፅ የምናየው ቂምና በቀልን ለቀጣይ ትውልድ የማውረስ ክፋት ተግባር ላይ ያተኮረ ሀውልት የመገንባት ተግባር ሲከናወን ነው፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን ለኛ ትተውልን ያለፉት ስራ የፋሲል ግንብ፤ የላሊበላንና የአክሱምን ድንቅ ጥበብ  ስራቸው እንጂ የቂም ሀውልት አልነበረም፡፡ እኛ ግን የነሱን ያህል ድንቅ የጥበብ ስራ መስራት ሲያቅተን፣ የቂምና የጥላቻ ሀውልት አውራሽ ሆነን ተገኘን፡፡ በቃ እኛ ልጆቻቸው የመጨረሻው ችሎታችንና፣ እውቀታችን እንዲህ ሆነ ቀረ? እስኪ ስለ እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ የኦሮሞ ህዝብ ዛሬ የቂም ሀውልት ነው የሚያስፈልገው ወይስ መሰረተ ልማት? የኦሮሞ ህዝብ የውሃ፤የጤና፤የመንገድ፤የመብራትና ዘመናዊ የግብርና ግብአት እንደሚያስፈልገው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የኛዎቹ የዛሬዎቹ መሪዎቻችን አሩሲ በ20% ሚልዮን ብር የቂም ማውረሻ ሀውልት ለአሩሲ ህዝብ በገፀ በረከትነት አቀረቡለት፡፡ የአሩሲ ህዝብ በዛሬዎቹ መሪዎቻችን ድርጊት እንዳፈረ ምንም አልጠራጠርም፡፡ የአሩሲ ህዝብ በድህነት ውስጥ እየኖረ በሃያ ሚሊዮን ብር የቂም ሀውልት ማውረስ ምን የሚሉት የአስተዳደር ስርአት ነው፡፡  
“የኢትዮ-ኤርትራ የቀን ግርዶሽ” መጽሐፍ ጸሐፊ ስለፍቅርና አንድነት ለማስተማር ድንበር ተሻግሮ ከዚህ ቀደም ከተለዩን የኤርትራ ሕዝቦች ጋር እንደገና ወደ ነበርንበት ሰላምና ፍቅር እንድንመለስ ለማድረግ የፃፈውን ፅሁፍ ስመለከት፤የታዘብኩት ነገር ቢኖር በተራው ዜጋና በመሪዎቻችን መካከል ሰፊ የአመለካከት መራራቅ መኖሩን ነው፡፡
በመጽሐፉ ምረቃ ዕለት ከመድረኩ ጀርባ ተለጥፎ የነበረው ጥቅስ እስካሁን ድረስ በልቤ ውስጥ ተሰንቅሮ ቀርቷል፡፡  ጥቅሱ የሚለው “ከወረስነው ቂም ይልቅ የምናወርሰው ፍቅር ይበልጣል” የሚል ነበር፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከወረሱት ጊዜያዊ ቂም ይልቅ የሚያወርሱት ፍቅር እንደሚበልጥ መሪዎቻችን አለማወቃቸው ያሳዝናል፡፡
የእኔ አባትና እናቴ የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው፡፡ እኔ የተወለድኩት አዲስ አበባ ነው፡፡ ነገር ግን እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ በአሩሲ በተሰራው የአኖሌ ሀውልት አፍረናል፡፡ አንገታችንም እንድንደፋ አድርጎናል፡፡
“የኢትዮ-ኤርትራ የቀን ግርዶሽ” መጽሐፍ ጸሐፊ እንደ ቼ ጉቬራ ከአገሩ ተሻግሮ ከሃያ ዓመታት በፊት የተለዩንንና ከ15 ዓመታት በፊት በአስከፊ ጦርነት ውስጥ ገብተን ከነበሩት የኤርትራ ሕዝቦች ጋር የእርስ በርስ ግንኙነታችን እንደገና ወደ ነበረበት ለመመለስና “ኖርማላይዜሽን” ለመፍጠር ያደረገው ጥረት ከልብ አስደስቶኛል፡፡
በግሌ፤ “የኢትዮ-ኤርትራ የቀን ግርዶሽ” መጽሐፍ ድንበርና ዘመን ተሻጋሪ ከመሆኑ በላይ ገዢዎቻችን መጽሐፉን አንብበው ቂም ከማውረስ ይልቅ ፍቅር ማውረስ የበለጠ እንደሆነ ሊያስተምር የሚችል በመሆኑ፣ እንዲያነቡት በዚህ አጋጣሚ በትህትና እጋብዛለሁ፡፡ የመጽሐፉ ጸሐፊ ለኔ የፍቅር፤የሰላምና የአንድነት ሰባኪ ታጋይ ከመሆኑ በላይ የዘነጋናቸውን የኤርትራ ሕዝቦችን ለማቀራረብ ጥረት በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል፡፡ እንደዚህ አይነት ጸሐፊዎች ይብዙልን፤ ይበርክቱልን እላለሁ፡፡

Published in ጥበብ

     ይቅርታ አንባብያን፡፡ የልብ ድካም ያለባቸው ሰዎች በተለይ ከፍቅር ጓደኞቻቸው ወይም ከትዳር አጋራቸው ሰርቀው ወሲባዊ ግንኙነት በሚፈፅሙበት ጊዜ የደም ብዛት አይሎ የልብ ምትም ፈጥኖ ህይወታቸው ያለፈበት አጋጣሚዎች ተመዝግበዋል፡፡ እስኪ የግለሰቦችን ታሪክ መነሻ እናድርግ ምናልባት የጉዳዩ አሳሳቢነት ወደኛ ቀርቦ ከታዬን፣
“ትውውቃችን ሁለት ዓመታት አስቆጥሮአል፣ ትላለች ወጣቷ ችግሯን ለመግለፅ ስትጀምር በእነዚህ ጊዚያት ውስጥ በቻልነው አጋጣሚና ባገኘነው ትርፍ ጊዜ እንገናኛለን፣ እንዋደዳለን፣ እንነፋፈቃለን፣ .  .  . ከእርሱ ጋር በማሳልፋቸው ጊዜያቶች ደስተኛ ነኝ፡፡ ሆኖም ሁኔታዎች ፈቅደው ወሲባዊ ግንኙነት ለመፈፀም ስናስብ ጓደኛዬ በጣም ይፈራል፣ ስሜቱ አይነሳሳም፣ ወሲባዊ ግንኙነት ከመፈፀም ይልቅ ከእኔ ጋር በሌሎች ጉዳዮች ጊዜ ማሳለፉን ይመርጣል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ያለፉትን ስድስት ወራት አሳለፍን፡፡ ጓደኛዬ ከእኔ በፊት ከሴቶች ጋር በጓደኝነት ከስድስት ወራት በላይ ባለበት ችግር ምክንያት አብሮ መቆየት አልቻለም፡፡ አሁን አሁን ስሜቴ እየቀዘቀዘ እያስፈራኝ መጣ . . .”
ሌላኛዋ ደግሞ ጓደኛዋ ራሱን ስቶ እርቃኑን መሬት ላይ ሲዘረገፍባት ላዩ ላይ ውሃ  ደፍታ፣ መስኮት በመክፈት አየር እንዲገባ በማድረግ የሆነውን ሁሉ ከሆነ በኋላ ለመረዳት እንደቻለች አስታውሳለች፡፡ በፀና የጓደኝነታቸው ወቅት ምንም እንኳን ከአደጋው በፊት ግንኙነት ቢኖራቸውም ይህ ክስተት ግን የመጀመሪያ እንደነበረና ከዚያ በኋላ እንደገና ወደ ግንኙነት ለመግባት ስጋት ውስጥ እንደወደቀ ትገልፃለች፡፡
ሰዎች ከተግባሩ በኋላ የሚያገኙት ውጤት ይለያይ እንጂ በአካላዊ እንቅስቃሴ (ስፖርት) እና በወሲባዊ ግንኙነት ወቅት የልብ ምት ፍጥነትና የደም ግፊት ይጨምራል፡፡ ለማነፃፀር ያህል በሰዓት ከሶስት እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር ሜዳ ላይ (ዳገትና ቁልቁለት ወይም ጭቃ በሌለበትና ወጣ ገባ ባልበዛበት መንገድ) በፍጥነት የሚራመድ ሰው ወይም 20 የፎቅ መወጣጫ ደረጃዎችን በአስር ሰከንድ የሚወጣ ሰውና አንዴ ወሲባዊ ግንኙነት የሚፈፅም  ሰው የልብ ምታቸውና የደም ግፊታቸው በእኩል ይጨምራል፡፡ ያም ሆኖ ግን ሁለቱ ሰዎች የሚገኙበት እድሜ፣ የሰውነት ክብደት፣ ያለባቸው ሱሶች (ለምሳሌ አጫሾች)፣ ከተግባሩ በፊት የተመገቡት ምግብና የወሰዱት መጠጥ  ወዘተ ሁኔታውን ሊለውጡት ይችላሉ፡፡
ወሲባዊ ግንኑነት የሁለቱን ተቃራኒ ፆታ የግንኙነት ጥልቀትና ጥብቅ መሆን የሚያመላክት ተግባር (ከሴተኛ አዳሪዎ ጋር የሚደረግ ግንኙነትስ?) ሲሆን ጤናማና የተሳካ ህይወት ለመምራትም ወሲባዊ ግንኑነት የራሱ ድርሻ አለው፡፡ አካልም መንፈስም የሚጠይቁት ጥያቄ አለ፡፡ ይህም ጤናማ ፍላጎት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው መጠጣትና መብላት እንደሚፈልገው ሁሉ በተመሳሳይ አካልና አእምሮም ወሲብ የመፈፀም ፍላጎት ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በእርግጥ ማንኛውም ሰው ይብዛም ይነስም፣ ጥራት ይኑረውም አይኑረውም .  .  .  ሳይበላና ሳይጠጣ መኖር አይቻለውም (ከተቻለም ከስድስት ሳምንታት ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ነው መዝለቅ የሚችለው ከዚያ በኋላ በህክምና መሞት ይጀምራል፣ ውሃን በተመለከተ ደግሞ ከሶስተ ቀናት እስከ አምስት ቀናት መቆዬት ይቻላል)፡፡ የወሲባዊ ግንኑነት ፍላጎትን ግን ለእድሜ ልክ ማቀብ ይቻላል፡፡ ሆኖም ይህ ለአብዛኞች የማይቻልና ህይወትንም ምልዑ ሊያደርግ የማይችል እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈልገው ጉዳይ ህይዎት ላይ ለህይዎት እጅግ አስፈላጊ የሚባሉ ዋና ዋና ጉዳዮች በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ ይህም ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ ለአንዱ አስፈላጊ የሚባለው ለሌላው ያንያህል ትርጉም የሚወስድ ላይሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ከፍላጎቱ ባሻገር ራስን መተካት ቤተሰብ ማፍራት በዚህም ደስታን መጨመር ብዙ ሰው ይፈልጋል፡፡
ከእነዚህ ምክንያቶች በመነጨ ታዲያ የልብ ህሙማንም ይኸው ፍላጎትና ስሜት ይኖራቸዋል፡፡ ሆኖም እንደማንኛውም የስፖርት እንቅስቃሴ ወሲባዊ ግንኑነትም የሰውነትን የልብ ምት ፍጥነትና የደም ግፊት ስለሚጨምር ግለሰቦቹ (ወንዶችም ሆኑ ሴቶች) አደጋ ላይ ሊወድቁ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ይከሰታሉ፡፡ አንዳንድ የትዳር አጋሮች ወይም የፍቅር ጓደኞች እንዲህ ያለ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ቶሎ ሊርቁ ወይም ሊለዩ ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ችግሩን በውስጣቸው አምቀው ለብቻቸው እየተብሰለሰሉ መለየትም አለመለየትም መሃከል ሆነው ይመሻል ይነጋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን መፍትሄ የሌለው ችግር አይደለም፡፡ በእርግጥ እርዳታ ወደሚገኝበት ማቅናት ያልቻሉ ሰዎች ድንገት ህይወታቸው በተቃራኒ ፆታ ጓደኞቻቸው እቅፍ ውስጥ ዝም ያሉ ተገኝተዋል፡፡ አንዳንድ ጥናቶች ግለሰቦቹ ከሞቱ በኋላ አስክሬናቸው ሲመረመር ለሞታቸው ምክንያት የልብ ድካሙና የደም ግፊቱ እንደሆነ ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ በመለስ ግን ድንገት ራሳቸውን ስተው የሚወድቁ ግን ለከፋ አደጋ የማይዳረጉ አብዛኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡
እንግዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ያለፉ ሰዎች ደግሞ ድጋሜ ወደ ወሲባዊ ግንኙነት ለመግባት ይቸገራሉ፡፡ ይፈራሉ፣ ጭንቀትና ድብርት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ስሜታቸው ይቀዘቅዛል (ይሞታል) አንዳንዴ ስንፈተ ወሲብ እስኪመስል  ይቀዘቅዛሉ፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ ይጎላል፡፡ ይበዛል፡፡ ልብ ድካም ያለባቸው ሰዎች በተለይ በስርቆት በሚፈፅሙበት ወሲባዊ ተራክቦ ምክንያት ብዙዎች ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ በመጀመሪያ በስርዎቱ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ ይህ ለልብ ምቱ ፍጥነት አስተዋፅዎ ያደርጋል፣ በሌላ በኩል በግንኙነቱ ምክንያት የልብ ምት ያይላል፣ የደም ግፊት ይጨምራል፡፡ በዚህ ምክንያት አደጋው ይሰፋል፡፡
በአካል እንቅስቃሴ የደም ግፊትና የልብ ምት ፍጥነትን ይጨምራሉ ብለናል፡፡ በዚህም በተለይ አካላዊ እቅስቃሴው ወሲባዊ ግንኙነትን የተመለከተ ከሆነ ግለሰቦች ለአደጋ ይጋለጣሉ ይባል እንጂ መፍትሄውም የሚወለደው እዚሁ ላይ ነው፡፡ እንቅስቃሴውን ከማድረግና ከመለማመድ፡፡ ብዙዎች ወደ ወደ ጤና ባለሞያዎች ከቀረቡ በኋላ ጤናማ የሆነ የወሲብ ህይወት (በዚህም ጤናማ የሆነ ትዳር) መምራት ችለዋል፡፡ በስነ ልቦና አማካሪዎቹ በኩልም በቃል ከሚሰጥ ሃሳብ ይልቅ በፁሁፍ የሚሰጣቸው የበለጠውን ውጤት አስገኝቷል፡፡ ይኽም የግለሰቦቹን ሁለንተናዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የሚቀርብ ነው፡፡
እንዲህ ያለ ችግር ያለባቸው ሰዎች መፍራት ያለባቸው ጉዳዩን አፍነው የሚይዙ ከሆነ ነው፡፡ በተረፈ ከፆታ ጓደኞቻቸው ጋር ፆታዊ ጉዳዮችን ማንሳትና መወያየት፣ ስለ ወሲባዊ ግንኙነታቸው በግልፅ ማውጋት፣ ግንኙነታቸውን ስለሚያውኩ ጉዳዮች ማንሳትና ያሉትን ችግሮች እንዴት መቅረፍ እንደሚችሉ ስልት ማበጀት፣ ከወሲባዊ ግንኙነት በፊት ከዚሁ ጋር የተያያዙ ወሬዎች ድርጊቶችን ለመፈፀም ግልፅ መሆን፣. . .፡፡ ከወሲባዊ ግንኙነት በፊት ከባድ ምግብ መመገብና አልኮል መጠጣትን ማስወገድ፣ የትንባሆ(ሲጋራ) ሱስ ካለ ማቆም ምንም አማራጭ የለውም (ማቆም የመፃፉን ያህ ቀላል ባይሆንም እንዴት ማቆም እንደሚችሉ የጤና ባሙያዎችን መጠጋቱ ወደ መፍትሄው ያደርሳል) ከዚህም ውጭ በግል ለባለ ጉዳዮቹ የሚቀርቡ መጠይቆችና ሃሳቦች ይኖራሉ (እነዚህን እውነቶች እንድፅፍፍ ሞያዬ ቢያስገድደኝም ባህል ይገድበኛል ሆኖም ችግሩ ያለበት ሰው በግል መረጃውን ቢፈልግ መደወል አቋራጩ ነው)፡፡ የፆታ ግንኙነት ምክር (sexual counseling) በዚህ ችግር ውስጥ ላሉ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ፍርሃትን ለማስወገድ፣ ፍላጎትን ወደነበረበት ደረጃ ለመመለስ፣ በዚህም የሚፈልጉትን ስሜት (ፍላጎት) እንዲያገኙ በጋራ ዘዴ ይቀየሳል፡፡ በጥቅሉም ጤናማ የሆነ ወሲባዊ ህይወትና ትዳር ይኖራቸዋል፣ በዚህም በሚፈልጉትን ደስታ እንዲያገኙ ያግዛል፡፡
ይህ ፅሁፍ መሰረት ያደረገው የተለያዩ ጥናቶችን መሆኑን ልጠቁም፡፡ ሳምንት እንገናኝ!

Published in ላንተና ላንቺ

       ንብረትነቱ የማሌዥያ የሆነው ኤም ኤች 370 የመንገደኞች አውሮፕላን እንደወጣ መቅረት፣ ዛሬም ቢሆን ሁላችንንም እያስገረመ ያለና የዘመናችን ያልተፈታ አዲስ እንቆቅልሽ ነው ማለት ይቻላል።
እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም ከማሌዥያዋ መዲና ኩዋላ ላምፑር ወደ ቻይናዋ ቤይጂንግ 239 ሲቪል መንገደኞችንና የአውሮፕላኑን ሰራተኞች አሳፍሮ ይበር የነበረው አውሮፕላን ከእይታ የተሰወረው በረራ በጀመረ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነበር።
ከአንድ ወር ከሳምንት በፊት ደብዛው የጠፋው ቦይንግ 777 አውሮፕላን ከጫናቸው መንገደኞች አብላጫ ቁጥር ያላቸው (153 ያህል ይሆናሉ ነው የሚባለው) የቻይና ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።
ይሄ ፅሁፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ አውሮፕላኑን ለማፈላለግ ከ24 በላይ ሃገሮች የተውጣጡ 60 የሚሆኑ አውሮፕላኖችና መርከቦች ቢሰማሩም፣ እስካሁን ድረስ ተስፋ ሰጪ ውጤት አልተገኘም። እንደውም ለረጅም ጊዜ በደቡባዊው የቻይና ባህር ላይ ይደረግ የነበረው ፍለጋ ወደ ደቡባዊው የህንድ ውቅያኖስ እስከዞረበትና አውስትራሊያ በሰፊው እስከተሳተፈችበት ጊዜ ድረስ ቅንጅት አልነበረውም ተብሎለታል።
ለመሆኑ የጠፋውን አውሮፕላን በማፈላለጉ ስራ ላይ ሃያሏ አሜሪካ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በስፋት ያለመሳተፏ ምክንያቱ ምን ይሆን? ይሄ አሁን አሁን ሁሉንም እያነጋገረ ያለ ጥያቄ ሆኗል። ይሄ ጥያቄ አሜሪካ ካላት የቴክኖሎጂ አቅምና በሌሎች መሰል አደጋዎች ካካበተችው ተሞክሮ አንፃር፣ ልታበረክተው የምትችለውን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሰነዘረ ነው።
የየሃገራቱ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክርና የፖለቲካ ጨዋታ ምናልባት የጠፋውን አውሮፕላን የጦስ ዶሮ አድርጎት ሊሆን ይችላልም እየተባለ ነው። ይህ አጭር ፅሁፍ እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን በመዳሰስ ለውይይት የሚሆኑ መነሻ ሃሳቦችን ለመሰንዘር ይሞክራል።
ከፍተኛና ውስብስብ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ያስፈልጉታል የተባለለት የአውሮፕላኑ ፍለጋ፣ የሃያሏን አሜሪካ ተሳትፎ ገና ከጅምሩ መጠየቁ ብዙዎችን ያሳመነ ይመስላል። ለዚህ ጉዳይ በዋናነት የሚነሱት ሙግቶች አሜሪካ ያሏትን እጅግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በእማኝነት ያስደገፉ ናቸው። አውሮፕላኑ ተሰወረ በተባለበት አካባቢ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች የተከማቹት የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑት እነዚህ መሳሪያዎች ለፍለጋው ስኬታማነት እጅግ ወሳኝ ናቸው መባሉም የቆዩ መሰል አደጋዎች በተከሰቱ ጊዜ የተገኘውን አመርቂ ተሞክሮ በዋቢነት በመጥቀስ ነው።  
በ2009 በደቡባዊው አትላንቲክ ዳርቻ የተከሰከሰውንና ንብረትነቱ የፈረንሳይ የሆነውን የ447 አውሮፕላን ስብርባሪና የድምፅ መቅረጫ ጥቁር ሳጥንን በባህር ጠላቂ ዘመናዊ ተ,ሐከርካሪዎቿ ለቃቅማ በማውጣት አለምን ያስደነቀችው አሜሪካ፣ በጠፋው የማሌዥያ ኤም ኤች 370 የመንገደኞች አውሮፕላን ፍለጋ ላይ በሙሉ ሃይሏ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎት ያለማሳየቷ በርግጥም ምን ምክንያት ቢኖራት ነው ያስብላል።
ከዚህ ጋር በተዛመደ ይህ ደብዛው የጠፋው አውሮፕላን ለአሜሪካኖቹ አንድ ዕድል ይዞላቸው እንደመጣም በሰፊው ይወራል። ከዓለማችን በቴክኖሎጂ እርምጃ የመጀመሪያው ጫፍ ላይ የምትገኘው አሜሪካ፤ በዘመናችን ብቅ እያለች የመጣችውን አዲሲቷን ተቀናቃኝ ሃገር፣ ቻይናን፣ ለመፈተን ከመፈለግ አንፃር ራሷን ከፍለጋው ያገለለች ይመስላል የሚለው ሚዛን የደፋ ጉዳይ እየሆነ ነው።
አሜሪካ፣ ቻይና ያመጠቀቻቸውን ሳተላይቶች ብቃት ለመፈተንና የዚያችው ሃገር ስሪቶች የሆኑ ሚሳይሎች ምናልባት በአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦቿ ላይ ሊያደርሱ ይችሉ ይሆናል ተብሎ የሚገመተውን ጥቃት ለመፈተሽ አጋጣሚውን እየተጠቀመችበት እንደሆነ ነው ዓለም እያወራ ያለው። “ዋንት” የተባለው የታይዋኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ዘጋቢ ኤሪክ ሺህ እንደሚለው፤ አሜሪካ የአውሮፕላኑን ፍለጋ ውጤታማ የሚያደርጉ የተሻሉና ብቁ የሆኑ የስለላ ሳተላይቶችና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ባለቤት ብትሆንም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምርጫዋ ዝምታ ብቻ ሆኖ ቆይቷል። እንደ ኤሪክ አባባል አሜሪካ የጠፋውን የማሌዥያ ኤም ኤች 370 አውሮፕላን በማፈላለጉ ስራ ላይ ላለመሳተፍ ስታንገራግር የቆየችው፣ የቻይና ሳተላይቶች ጉዳዩን አስመልክተው የሚያቀርቡትን ምስጢራዊ መረጃ ለማወቅ ከመፈለግ የተነሳ ነው።
ይሄ ጉዳይ ሌላውን የዘመናችንን ሀቅ እንድናስታውስም ያደርገናል። የሶማሌዎችን የባህር ላይ ውንብድና ለመከላከል በሚል በሰሜናዊው የህንድ ውቅያኖስ ላይ የተሰባሰቡት ሃገሮች፣ ሃያላኑን ጨምሮ፣ ፋታ ባገኙ ቁጥር በእርስ በእርስ ስለላና የፍተሻ ቁጥጥር ራሳቸውን ወጥረው መገኘታቸው፣ አሁን እያወጋን ስላለው ታላቅ የመሆን ፉክክር አንዱ ማሳያ ነው።
ብቅ ጥልቅ እያሉ በአካባቢው የሚጓዙ መርከቦችን ሳይታሰብ በድንገተኛ ጥቃቶቻቸው የሚያስደነግጡትን የምስራቅ አፍሪካ ዘራፊዎች ለማደን ግንባር የፈጠሩት እነዚህ ጉልበተኛ ሃገሮች፣ የባህር ላይ ወንበዴዎቹ ጥቃት ጋብ ሲልላቸው የሚያደርጉት የእርስ በርስ የመፈታተሸ ወይም የመሞካከር ባህሪያቸው፣ ጅብ ሲመጣ ግንባር እንደሚፈጥሩትና ሲሄድ ደሞ እንደሚነካከሱት ውሾች ዓይነት ይመስላል።
እነዚህንና መሰል የዓለማችን ሃያላን ሃገራትን የጎሪጥ መተያየት ምክንያት በማድረግ ነው፣ ሮይተር በመጋቢት 28፤ 2014 ዕትሙ “በጂኦ ፖለተካዊ ጨዋታ ፍለጋው የተስተጓጎለው ኤም ኤች 370 የመንገደኞች አውሮፕላን” በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ ያቀረበው።
ሌላው አሜሪካንን በፍለጋው ላይ ወሳኝ ሚና ልትጫወት ትችላለች የሚያስብለው ምክንያት ወደ ጠፈር ያስወነጨፈቻቸው መረጃን የሚያቀብሉ ዘመናዊ ሳተላይቶች ባለቤት መሆኗ ነው። ሚያዚያ 6፣ 2012 አሜሪካ ከካልፎርኒያ ቫንደርበርግ የአየር ሃይል ጣቢያ የተኮሰችውና NROL-25 የሚል ስያሜ የተሰጠው የስለላ ሳተላይት ቀን  ለሊት ሳይል ጥቅጥቅ ደመናዎችን ሰንጥቆ በማለፍ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወታደራዊ ምሽጎችን፣ ተፈላጊ ዒላማዎችንና ሌሎችንም ተንቀሳቃሽ አካሎችን የማየት ሃይል እንዳለው ይነገራል። ይሄ በምስጢር ወደህዋ የተወነጨፈው ሳተላይት፣ በመቶ ማይሎች ከሚቆጠር ርቀት ላይ የሚገኙና በመጠን ያንድ ትልቅ ሰው ቡጢን የሚያህሉ አናሳ ነገሮችን እንኳን ሳይቀር እጅግ አጉልቶ የማሳየት ብቃቱ አስደናቂ ነው ተብሎለታል።
ይሄም ብቻ አይደለም። ይችው የዘመናችን ሃያል ሃገር አሜሪካ፣ በታህሳስ 2013 NROL-39 በሚል ስያሜ የሚጠራ አዲስ የስለላ ሳተላይት ወደ ህዋ ልካለች። አዲሱ ሳተላይት ከረጅም ርቀት ላይ ሆኖ በምድር ላይ ያሉ ተፈላጊ ነገሮችን መንጥሮ የማንሳት ችሎታው፣ ኦክታፐስ የሚል ስያሜን አሰገኝቶለታል። ይሄ የባህር ዓሣ ዝርያ፣ ኦክታፐስ፣ በርካታ እግርና እጆቹ ያሻውን የባህር ላይ አውሬ በቀላሉ ለመጥለፍ እንደሚያስችሉት ሁሉ፣ አዲሱ ሳተላይትም በተመሳሳይ ክንውኑ የሱን ስም እንዲወስድ ተደርጓል። የአሜሪካ ጠላት የሆነ ሁሉ፣ የትም ሆነ የት (ምጥ ይግባ ስምጥ) ከዚህ ሁሉ በእጁ ከሆነ ዘመናዊ የስለላ ሳተላይት እይታ ውጭ መሆን አይችልም። ራሳቸው አሜሪካኖቹ የመሳሪያውን ብቃት አስመልክተው ሲናገሩ nothing is beyond our reach ይላሉ።
እንግዲህ የዘመናችን ጉልበተኛዋ ሃገር፣ አሜሪካ፣ እነዚህንና መሰል ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ታጥቃ ነው ደብዛው በጠፋው በኤም ኤች 370 አውሮፕላን ፍለጋ ላይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ላለመሰማራት የፈለገችው። ከጥቂት ቀናት በፊት በባህር ሃይሏ በኩል በፍለጋው ላይ መሳተፍ እንደጀመረች መረጃዎች ቢጠቁሙም፣ ብዙዎች ስለ ውጤታማነቱ ይጠራጠራሉ። የአሜሪካን ተሳትፎ “ከልብ ያልሆነ ወይም ካንገት በላይ የሆነ የዘገየ ተሳትፎዋ” በሚል ሌላው አሜሪካንን ባውሮፕላኑ ፍለጋ ላይ ውጤታማ ሚና ልትጫወት ትችላለች የሚያስብለው ሙግት አሳማኝ የሚሆነው ባካባቢው ባላት ወታደራዊ ጣቢያ ውስጥ ባደራጀቻችው ከፍተኛ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎቿ ብቃት ነው።
ንብረትነቱ የማሌዥያ የሆነው ኤም ኤች 370 የመንገደኞች አውሮፕላን ጠፋ በተባለበት ደቡባዊው የህንድ ውቅያኖስ ላይ አንዲት የውስጥ እግር ምስል ያላትና ዲያጎ ጋርሺያ እየተባለች የምትጠራ ደሴት ትገኛለች። ይህች ደሴት እ.ኤ.አ. እስከ 1966 ድረስ በእንግሊዝ ንብረትነት ተይዛ እንደቆየች ይነገራል። እንግሊዝ በጦር መሳሪያ ግዢ ሰበብ አሜሪካ ላይ የነበረባትን የ14 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ለማካካስ በሚል ነበር አሜሪካ ደሴቲቱን ለወታደራዊ ግልጋሎት እንድትጠቀምበት የፈቀደችላት። ሃያሏ ሃገር አሜሪካ ደሴቲቱን እንደተረከበች በውስጧ የሚኖሩትንና ቁጥራቸው 2,000 የሚሆነውን ቻጎሳውያን በድብቅ አፍሳ በ1,200 ማይልስ ርቀት ላይ ወደሚገኙት ሞሪሺየሰና ሲሺየልስ በጀልባ በማጓጓዝ አስፍራቸዋለች። አሜሪካ ያንን ብቻ በማድረግ አልተገታችም። የቻጎሳውያኑን ውሾችም ሰብስባ ነዋሪዎቹ ዓይናቸው እያየ በመርዝ ጋዝ አጋይታቸዋለች። ጉዳዩ ከዓለም ሕዝብ እይታ ተሰውሮ ይቆይ ዘንድ ሙከራ ቢደረግም፣  በአሜሪካ የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ‘Island of Shame’… ወይም “የቅሌቱ ደሴት፣ የዩ. ኤስ. አሜሪካ ወታደራዊ ምስጢር በዲያጎ ጋርሺያ” በሚል ርዕስ በተፃፈ መፅሐፍ ሊጋለጥ ችሏል።
በደሴቲቱ የተቋቋመው ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ጠፈር ጠቃሽ የቅኝት መሳሪያዎች ከተከማቹባቸው በጣት ከሚቆጠሩ የዓለማችን ወታደራዊ ጣቢያዎች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል። ዛሬ የዲያጎ ጋርሺያ ወታደራዊ ደሴት ቢ-52ና ቢ-2ን የመሳሰሉ እጅግ ዘመናዊ ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖችን ጨምሮ፣ ሌሎች የጦር መሳሪያ ክምችቶችና የስለላ መሳሪያዎች የሚገኙበትና አሜሪካ አሏት ከሚባሉት 1,000 መሰል የጦር ሰፈሮች አንዱ፣ ምናልባትም ዋንኛው እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አሜሪካ ይሄን በወታደራዊ የመጓጓዣ ዘዴ ብቻ የሚደረስበትን ደሴት፣ አፍጋኒስታንንና ኢራቅን ለመደብደብ መነሻና መድረሻ አድርጋ ከመገልገሏም በላይ፣ በሽብር ወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችንም ለማሰርና ለማሰቃየት እንደምትጠቀምበት ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። ወታደራዊ ጣቢያው ውቅያኖስ ወለል ድረስ ጠልቀው በመግባት ብረት ነክ ነገሮችን መልቀም የሚችሉ መሳሪዎች እንደተከማቹበትም ታውቋል።
ታዲያ በፍለጋው ላይ ከጅምሩ አንስቶ በሙሉ ልቧ አሜሪካ ተሳትፋ ቢሆን ኖሮ፣ ያ የጠፋው  የማሌዥያ አውሮፕላን በቅርብ ርቀት በዲያጎ ጋርሺያ ላይ ከሚገኙት የስለላ መሳሪያዎች እይታ ውጭ ይሆን ነበር? ብለው ይጠይቃሉ- ታዛቢዎች።
ከአመታት በፊት ተመሳሳይ የብልጣብልጥነት ልግመት ወይም ቸልተኝነት ከአሜሪካ በኩል ተስተውሎ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በታህሳስ 2004 በህንድ ውቅያኖስ ላይ ተከስቶ የነበረው የሱናሚ አደጋ ለዚህ እንደማሳያነት ይጠቀሳል። የአሜሪካ ብሔራዊ የአየር ንብረት አገልግሎት ተቋም ቃል አቀባይ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ማረጋገጫ፤ የሱናሚ አደጋው በታህሳስ 26፣ 2004 የሴሪላንካንና የታይላንድን የባህር ዳርቻዎች ከመምታቱ አስቀድሞ፣ የተቋሙ የሃዋይ ማዕከል ለዋሺንግተንና በዲያጎ ጋርሺያ ደሴት ላይ ለሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ምልክት ማስተላለፉን አስታውቋል። ቃል አቀባዩ አክሎ እንደተናገረው፣ የዲያጎ ጋርሺያው ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ሃላፊዎች ባካባቢው ላሉ ሃገሮች ተመሳሳይ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መልእክት ስለማስተላለፋቸው የታወቀ ነገር የለም።
ያም ሆነ ይህ፣ ሃያሏ አሜሪካ ማድረግ የምትችለውን ብቻ ሳይሆን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን የፍለጋ ትብብር አስቀድማ በሙሉ ልቧ ለማድረግ ባለመፍቀዷ የማሌዥያው አውሮፕላን እስካሁን ድረስ የደረሰበት ሳይታወቅ ቀርቷል።
አሁንም ቀኖች እየነጎዱ በሄዱ ቁጥር፣ የዚህ አውሮፕላን ጠፍቶ መቅረት ሁሉንም ሰብአዊ ዜጋ እንዳስጨነቀው ነው። ከጎረቤት ሃገሮች ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ የራዳር መረጃዎችን ለማግኘት እንኳን ያልታደለችው ማሌዥያ፤ ግራ በተጋባ ሁኔታ ውስጥ ስትገኝ፣ ደብዛው የጠፋው አውሮፕላኗ ደሞ በድብቁ ያካባቢው የፖለቲካ ጨዋታ ሰበብ ወጥመድ ላይ የተጣለ ቁራጭ ስጋ ሆኖ የቀረ ይመስላል።

Published in ከአለም ዙሪያ

የአዲስ አበባ ከተማ አሁን የሚሰራላት አስረኛው ማስተር ፕላን መሆኑን ሰምቻለሁ …  
አዲስ አበባ ያለ ፕላን በዘፈቀደ የተቆረቆረች ከተማ ነች፡፡ ጣይቱ እንጦጦ ላይ ሆነው ፍል ውሃን ሲያዩት “ፍል ውሃ ሞቃት ነው፤ ከእንጦጦ ብርድ ይሻላል” በማለት ከንጉሡ ጋር ተማክረው ነው፣ አሁን ቤተመንግስት ያለበት አካባቢ የሠፈሩት፡፡ ከዚያም ከተማዋ መስፋፋት ቀጠለች፡፡ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ፕላን እንግዲህ የእቴጌ ጣይቱ ፕላን መሆኑ ነው፡፡  
ከምኒልክ በኋላ ዘመናዊ የከተማ ፕላን የምንለውና  እንደመነሻ የምንወስደው በጣሊያን ጊዜ የተሠራውን ነው፡፡ ከጣሊያን በኋላ እንግሊዞች የራሳቸውን ሙከራ አድርገዋል፡፡ ከዛ በኋላ የተለያዩ ፕላኖች ተሰርተው፣ አሁን በስራ ላይ ያለው የማስተር ፕላን ላይ ደረስን፡፡ ይሄ ማስተር ፕላን በመጪው ግንቦት ወር የአገልግሎት ጊዜው ይጠናቀቃል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት፣ በዚህ ማስተር ፕላን ምን ሠራን? ምን አገኘን? ምን ጥቅም ነበረው? በሚል የፋይዳ ግምገማ ተካሂዷል፡፡ የጥናቱ ውጤትም የተወሰኑ ችግሮች እና ጥሩ ጎኖች እንደነበሩት ጠቁሟል፡፡ ኢአይቢሲ የሚባል ድርጅት ከ“ኢትዮጵያን ስተዲስ ኦፍ አርኪቴክርቸስ ቢዩልዲንግ ኮንስትራክሽንና ሲቲ ፕላኒንግ” (የህንፃ ኮሌጅ የምንለው) በመሆን ነው በጋራ ያጠኑት፡፡ ወደ መሪ ፕላኑ ስንመጣ፣ የፈረንሳይዋ ሊዮን ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር የእህትማማቾች ከተማ ሰነድ ፈርማለች፡፡ በዚህም የተነሳ ባለን ግንኙነት “ማቲዎስ ኮንሰልት” ከሚባል የግል አማካሪ ድርጅት ጋር በስራ ላይ ያለው መሪ ፕላን ምን ጠንካራና ደካማ ጐኖች እንዳሉት ተገመገመ፡፡ ነባር መንገዶች የተሻሻሉበት፣ አዳዲስ መንገዶች የተሠሩበት፣ እና ሌሎችም እንደጠንካራ ጐን የተጠቀሱ ሲሆን ደካማ ጐኑ ደግሞ የከተማ ፕላኑ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ማተኮሩ ነው፡፡ የአዲስ አበባ እድገት፣ በኦሮሚያ ከተሞች ላይ ስላለው ተፅዕኖ ምንም አይልም፡፡ ከከተሞች ጋር ብቻ ሳይሆን ከገጠር አካባቢው ጋር ምን አይነት መስተጋብር መፈጠር እንዳለበት ፕላኑ አላመላከተም፡፡ ይሄ በቅጡ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ቢዘጋጅ ኖሮ በአካባቢው ያሉ ገበሬዎች ከአዲስ አበባ የተሻለ እድገት መጠቀም ይችሉ ነበር፤ ሆኖም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡ አዲስ አበባም ከእነዚህ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች ጋር በአግባቡ ተሳስሮ መጠቀም ይችል ነበር፡፡ ይህ ግን ተግባራዊ አልሆነም፤ የሚል ግምገማ ነበር የተደረገው፡፡
አዲስ አበባ የኦሮምያ ልዩ ዞን ከተሞችን ትጠቀልላለች የሚል ስጋት በስፋት እየተንፀባረቀ ነው … እርስዎስ ምን ይላሉ?
አዲስ አበባ ተስፋፍቶ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችና አካባቢዎችን ይጠቀልላል የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ የአዲስ አበባ የተወሰኑ ክ/ከተሞች ወደዛ አስተዳደር ይሄዳሉ ማለትም አይደለም፡፡ ነገር ግን በማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ ያየን እንደሆነ፣ አንድ አካባቢ ሲለማ በዙሪያው ካሉ አካባቢዎች ላይ ተፅዕኖ ማምጣቱ አይቀርም፡፡ አንድ አካባቢ ተሳስሮ መልማቱ ለሁሉም በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ በዙሪያዋ ካሉ የገጠር አካባቢዎች ነው ብዙ ነገሮችን የምታገኘው፡፡ ውሃ፣ የማገዶ እንጨት … ይጠቀሳሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከብት እያረቡ የሚኖሩ ሰዎች የከብት መኖ የሚያገኙትም በመዲናዋ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ነው፡፡ የወተትና የአትክልት አቅርቦት የመሳሰሉትም የሚመጡት በዙሪያዋ ካሉ ከተሞች ነው፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ግን አይደለችም የምትጠቀመው፡፡ በዙሪያዋ ያሉ ከተሞችም በስራና በትምህርት ዕድል እንዲሁም በትራንስፖርት አገልግሎት ይጠቀማሉ፤ በብዙ ነገር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይሄ ትስስር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች በአግባቡ አስበውበትና አቅደው፣ ምን እንጠቀም? እንዴት በጋራ እንልማ?… የሚል አቅጣጫ ተይዞ በጋራ እየተንቀሳቀሱ አይደለም፡፡ በእርግጥ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩና ግንኙነቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡ እንዲህ ያለው አሰራር  እኛ ጋ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ በሌሎች አገሮች ከተሞችም የሚከተሉት አሰራር ነው፡፡ በአንድ በኩል ስናየው፣ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ይሄ ዓይነት ጉዳይ ብዙም አሳሳቢ አልነበረምና አልተነሳም፡፡ አሁን ግን የከተማው እድገት እንዲነሳ ፈቅዷል፡፡ እንደሚታወቀው ከከተማ እድገት ጋር የሚመጡ አዎንታዊም አሉታዊም ነገሮች አሉ፡፡
የተቀናጀ የጋራ ፕላኑ በጋራ የማልማት ሳይሆን ድንበር የማካለል ዓላማ ያለው ነው የሚሉ ወገኖች አሉ …
የማካለል ስራ አይደለም፡፡ በተጨባጭ ሲታይ እኮ አዲስ አበባ ብቻዋን አይደለም እያደገች ያለው፡፡ በዙሪያዋ ያሉ ከተሞችም እያደጉ ነው፡፡ አዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉት ከተሞች የየራሳቸውን ፕላን ሰርተው ሳይናበቡ በየግል ሲንቀሳቀሱ ነው የቆዩት፡፡ ለምሳሌ ሱሉልታ ከቡራዩ ጋር ድንበር ይዋሰናሉ፤ ምንም እንኳን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ቢሆንም፡፡ ቡራዩ ደግሞ ከሰበታ ጋር፣ ሰበታ ከአቃቂ ቃሊቲ፣ አቃቂ ቃሊቲ ዱከም ገላን ዞሮ ከለገዳዲና ከለገጣፎ ጋር ይገናኛል፡፡ እንዲህ እያለ እስከ ሱሉልታ ይሄዳል፡፡ ክብ ይሠራል ማለት ነው፡፡
እነዚህ ከተሞች እርስ በርሳቸው ተናበዋል ወይ ብለን ስንጠይቅ፣ ጥናታችን እንደሚጠቁመው  አልተናበቡም፡፡ አዲስ አበባስ ከእያንዳንዳቸው ጋር ተናቧል ወይ ሲባል አሁንም አልተናበበም፡፡ ስለዚህ መፍትሔው የተቀናጀ ፕላን ነው፡፡
በፕላን አሰራር ሁለት ደረጃዎች አሉ፡፡ የዕቅድና የአፈፃፀም ደረጃ ይባላሉ፡፡ ይሄንን  ሥራ ጋር ለአገር አቀፍ ወይም ለአለም አቀፍ ተቋራጭ አማካሪ ሰጥተው ማሰራት ይችላሉ፡፡ አሁን እንደተደረገው በጋራ ፕሮጀክት ጽ/ቤትም ማሠራት ይችላሉ፡፡ ወደ አፈፃፀም ሲመጣ፣ የትኛውም የአስተዳደር አካል የሚያስፈጽመው በህግ በተቀመጠለት ድንበር ነው፡፡ መጀመሪያ የፕላን ክልል ነው የተወሰነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ በቀጥታ ተፅዕኖ የሚያሳድሩና ከተማዋ ተፅዕኖ የምታሳርፍባቸው የገጠር አካባቢና ከተሞች የትኞቹ ናቸው? ተብሎ በጥናት ተለየ፡፡ በዚህ መሠረት የፕላን ሪጂን (ክልል) ተሠመረ፡፡ የፕላን ክልል ማለት የአስተዳደር (የፖለቲካ) ክልል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች በኢኮኖሚ ተሳስረው እየለሙ ነው፡፡ ሁሉም ግን ራሳቸውን የቻሉ ሉዓላዊያን መንግስታት ናቸው፤ ግን የሚጋሩት ደግሞ አለ፡፡ የኢኮኖሚን ዕድገት ለማፋጠን፣ ንግድና ልማትን ለማቀላጠፍ በጋራ ይሠራሉ፡፡ ይሄ የተለመደ አሰራር ነው፡፡
ለምሳሌ ከአዲስ አበባ አዳማ የተሠራውን ፈጣን መንገድ እንውሰድ፡፡ መንገዱ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው ያለው፡፡ እና የፕላን ክልሉ ተወሰነ፡፡ ይሄ አጠቃላይ ሁኔታውን የሚያሳይ መርህ ነው፡፡ በኦሮሚያ ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት የተሠራውን ፕላን አመጣን፡፡ ከአዲስ አበባ ጋር ሲታይ ምን ይመስላል? ምን ቢጨመርበት ጥሩ ነው? የሚሉትን አየን፡፡ ይህ ፕላን እንዴት ይፈፀም? ሲባል ሁሉም በህገመንግስቱ በተቀመጠለት ድንጋጌ መሰረት አዲስ አበባም፣ ሰበታም፣ ዱከምም፣ ገላንም፣ የየራሳቸውን ፕላን ያስፈጽማሉ፡፡
በጋራ የሠራነው ፕላን ግን እየተናበበ ነው መፈፀም ያለበት፤ ይኼው ነው፡፡ ትራንስፖርትን በጋራ ካልሠራን፣ ትንንሾቹ ከተሞች ከአዲስ አበባ ጋር ተቀናጅተው የትራንስፖርት አገልግሎት ካላገኙ ለብቻቸው የሚወጡት አይሆንም፡፡ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎን የመስራት አቅም የላቸውም፡፡
በኦሮሚያ ልዩ ዞን 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶ አደሮች ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ ከተሜነትን የተላበሰ ገበሬ እንዲፈጠር ይፈልጋል፡፡ ሁለቱ እንዴት ነው የሚታረቁት?
የመሬት አጠቃቀም ፕላናችንን ማጣጣም አለብን፡፡ በጋራ መስራት የሚገቡንን ጉዳዮች ተቀናጅተን መስራት አለብን የሚል ነው እንቅስቃሴው፡፡ ይሄ ደግ ትልቅ አገራዊ ጠቀሜታ አለው፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዋና ከተማ ናት፡፡ የአፍሪካ ህዝቦችም ዋና ከተማ ናት፤ አለማቀፋዊ ባህሪ አላት፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ ቦታ እንዲኖረን፣ ተቀባይነት እንድናገኝ መወዳደር አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ተቀናጅተን መሆን አለበት፡፡
ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሩ ለስደትና ለሥራ አጥነት ይጋለጣል የሚሉ ወገኖች ስጋት አላቸው …
1.3 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በሙሉ የከተማ ልማት ያሰጋቸዋል ማለት አይደለም፡፡ የተቀናጀ ፕላኑ አርሶ አደሮቹን ሁሉ ያጠፋቸዋል የሚል ግምትም የለንም፡፡ እኛ እያልን ያለነው ከተሞች ያለ አግባብ አይንሰራፉ ነው፡፡ አዲስ አበባ ያለ አግባብ መንሰራፋት የለባትም፡፡
አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ጋር ትስስር እንፍጠር ያለችው መሬት ፍለጋ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ …
አዲስ አበባ ከተማ ለማደግ የሚያስፈልገው መሬት የለውም ማለት አይደለም፡፡ በዋናነት ለአዲስ አበባ  የመሬት ምንጭ የሚሆነው፣ በመልሶ ማልማት የሚገኘው ነው፡፡ አዲስ አበባ ከ25-30 ዓመት ድረስ እስከ 8 ሚሊዮን ህዝብ ሳትቸገር መያዝ ትችላለች፡፡ ግን ዙሪያ ከተሞችም ቢሆኑ እየተስፋፉ ነው ያሉት፡፡ ደግሞ ወደ አርሶ አደሩ የእርሻ ቦታ ነው እየተስፋፉ ያሉት፡፡  በፕላኒንግ ሪጅን ውስጥ 85 በመቶው የእርሻ ቦታ ይሁን፤ 15 በመቶ ብቻ ለከተሞች ይተው ብለናል፡፡
ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ “ገበሬዎች ይፈናቀላሉ” ለሚለው በመስፋፍያ አካባቢ ያሉ ገበሬዎች ተገቢው ካሣ ተሰጥቷቸው ይነሳሉ፡፡ ገበሬዎቹ የከተማው አካል እንዲሆኑ ስራ ተሰርቷል ወይ የሚለው ሊያነጋግር ይችላል፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከተሞች ላይም እንዲሁ ነው፡፡ ከተሞች ወደ ገበሬው ይሂዱ ሳይሆን ከተሜነት ገበሬው ጋ ይሂድ የሚል መርህ ነው የምንከተለው፡፡ ይህን ስንልም የገጠር የእድገት ማዕከላት አሉ፤ አገልግሎት ሊሰጥባቸው የሚችሉ፡፡ እነዚህ ላይ ትኩረት አድርገን እንስራ፤ ዝም ብለን የምንጠቀምበት ከሆነ እኮ መሬት ያልቃል፡፡ እንደ ናሙና የወሰድናት የገጠር  የእድገት ማዕከል አለች፤ ሰበታ ውስጥ ያጠናናት፡፡
ዋናው ነገር … የኤሌክትሪክ ሃይል ለማግኘት መንደሮች መጠጋጋት አለባቸው፡፡ ገበሬው አገልግሎት ማግኘት አለበት፡፡ የብድርና የፋይናንስ አገልግሎቶች… የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ለልጆቹ ይፈልጋል፤ ማግኘትም አለበት፡፡ እነዚህን የሚያገኘው ግን ከ30 እና 40 ኪሎ ሜትር ርቀት እየተጓዘ መሆን የለበትም፡፡ እነዚህ የነገ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ማዕከላት ናቸው፡፡ ገበሬው ሙሉ በሙሉ ከግብርና ጥገኝነት የሚላቀቅበት መንገድ ይሄ ነው፡፡ ገበሬው በተሰጋው መጠን ይፈናቀላል የሚል ስጋት የለም፤ ምክንያቱም የከተማ ቦታ (ክልል) ሙሉ በሙሉ በፕላን ይመራና ይከለል እያልን ነው ያልነው፡፡
እስከአሁን በነበረው ሁኔታ የተወሰኑ ሰዎች ችግር ሊገጥማቸው ይችል ነበር፤ አሁን ግን ከተሞች በፕላን የሚመሩ ከሆነ፣ ገበሬው አይፈናቀልም፡፡ በፕላን ክልል ደረጃ እስከ አዳማ ድረስ ይሄዳል፡፡ ይሄ ማለት አዲስ አበባ አዳማ ድረስ ሄዳ ታስተዳድራለች፤ የቀን ተቀን ጉዳይ ውስጥ ትገባለች ማለት አይደለም፡፡ ግን ትስስሩ ተፈጥሯል፡፡ በአዲሱ መንገድ ከአዲስ አበባ አዳማ 45 ደቂቃ ብቻ ነው የሚፈጀው፡፡ ስለዚህ ግንኙነቱና ትስስሩ ይበልጥ እየተቀላጠፈ ነው፡፡
ሞጆ ላይ ኤርፖርት ለመስራት ታስቧል፡፡ የደረቅ ወደብም አለ፡፡ ይሄ የአዲስ አበባንም የአዳማንም ነጋዴ የሚያስተሳስር ነው፡፡  የአዳማው መንገድ የሚቀጥል ነው፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ፍራንክፈርት ነው ወይስ ከአዲስ አበባ አዋሳ ነው የሚቀርበው? ሲባል፣ በትራንስፖርቱ ፈጣንነት የተነሳ ከአዲስ አበባ ፍራንክፈርት ይቀርባል፡፡ ከአንድ ሁለት ዓመት በኋላ ግን በሚዘረጋው አዲስ መንገድ፣ ከአዲስ አበባ አዋሳ በጣም ይቀርባል፡፡ በቀጥታ አዲስ አበባን፤ ገላንና ዱከምን፤ በደቡብ ምዕራብ በኩል ሰበታን፣ በሰሜን ምዕራብ በኩል ቡራዩንና መናገሻን አስተሳስሮ፣ በሰሜን በኩል ሱሉልታን፣ ጫንጮን … ያስተሳስራል፡፡ ይህ በፕላን  ክልሉ ውስጥ ነው ያለው፡፡
በሌላ አቅጣጫ ለገዳዲ ለገጣፎ ድረስ ይሄዳል፡፡ የመዋቅራዊ ፕላንና የመሬት አጠቃቀም በከተማ ደረጃ የሚሠራለት ነው፡፡ አዲስ አበባ የራሱን በራሱ ክልል፣ በምክር ቤት ደረጃ በአዋጅ ማፀደቅ አለበት፡፡ የፖለቲካና የህግ ጉዳይ አለው፡፡ በኦሮሚያም በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚወሰን ነው፡፡ ከተሞቹ የየራሳቸውን ፕላን ራሳቸው ያፀድቃሉ፡፡ የጋራ ጉዳይ ላይ ግን በጋራ ያጠናሉ፡፡
አንዳንዶቹ ከኢትዮጵያ ወደ አለማቀፍ ሁኔታዎችም የሚያራምዱ አሉ፡፡ አዲስ አበባ አስር ክፍለ ከተሞች አላት፡፡ አስሩም ክፍለ ከተሞች የዛሬ አስር አመት ከነበሩበት እያደጉ ነው፡፡ የቆዳ ስፋቱ ሳይጨምር የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ትልልቅ ክ/ከተሞች ስላሉ፣ አዲስ አበባ ከ10 ወደ 15 ክ/ከተሞች ማደግ እንዳለባት ያደረግነው ጥናት ያመላክታል፡፡
መቼ ወደ ተግባር የሚገባ ይመስልዎታል?
ፕሮጀክቱን የሚመሩ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ አመራር አካላት አሉ፡፡ የቦርዱ መሪ የአዲስ አበባ ከንቲባ ናቸው፡፡ ምክትል ሰብሳቢ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ሁሉም አመራር አካላት ህዝቡን የማወያየት ስራ እየሰሩ ናቸው፡፡ በቢሮዎች፣ በከተሞች፣ በወረዳ፣ በዞንና በየክ/ከተማው ደረጃ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ ከመጽደቁ በፊት ግብአቶች እንወስድና በቅርቡ እንዲፀድቅ ጥረት እናደርጋለን፡፡
በአዳማው የአሠልጣኞች ስልጠና ላይ የተቀናጀ የጋራ ልማቱ በምን በጀት ነው የሚሠራው የሚለው እንደ ስጋት ሲነሳ ነበር …
የገቢ ሁኔታ ከተነሳ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እኮ ነው የምንሠራው፡፡ ከፍተኛ የመሬት አቅርቦት እጥረት አለ፡፡ የመንግስት የታክስ መሠረቱ የሚሰፋበትና ገቢዎች የሚያድጉበት ሁኔታ በጥናቱ ተቀምጧል፡፡ ለልማት የሚሆኑ መሠረተ ልማቶች ከተዘረጉ፣ ልማቱ ሲመጣ ገቢ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ የበጀት ስጋት አይኖርም፡፡
በፕላኑ የተቀመጡ የመሠረተ ልማት እቅዶችን በተመለከተ አንዳንድ ወገኖች፣ “ሊጨበጡ የማይችሉ ህልም የሚመስሉ ናቸው” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል…
መጀመሪያ ላይ እኔም የሚጨበጥ አልመሰለኝም ነበር፤ በኋላ ግን ስናየው ይቻላል፡፡ እንደ ምሳሌነት የምንጠቅሰው የህዳሴውን ግድብ ነው፡፡ አይቻልም ተብሎ ነበር፡፡ አባይን ኢትዮጵያ አትገድበውም ሲባል ነበር ግን ተችሏል፡፡ ፕላን ሲሰራ በደንብ ሰፋ ተደርጐ ነው የሚሠራው፡፡ አንድ ታዋቂ የአሜሪካ አርክቴክት ምን ይላል መሰለሽ? “ትንሽ ፕላን አትስሩ፤ የሰዎችን ደም (ስሜት) የሚነሽጥ ፕላን ስሩ፤  ፕላን ትንሽ ሲሆን ያለመፈፀም ሁኔታ ይገጥመዋል” ይላል፡
ባለሙያው ብዙ የአሜሪካ ከተሞችን ፕላን የሠራ ነው፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕሮጀክት መሪ ፕላን፣ ለቀጣዩ 25 እና 30 ዓመት ለአገር እድገት ወሳኝ ነው፡፡ 

Saturday, 26 April 2014 12:40

ከጥሎሽ የሚቀድም ጥሎሽ

       የሰርግ ወቅት ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ኩለው የሚድሩበት፣ ጥንዶች የሚሞሸሩበትና ሆቴሎች፣ መናፈሻዎችና መንገዶች በሙሽሮች የሚጨናነቁበት የሰርግ ወቅት፡፡ እንዲህ እንደዛሬው ተጋቢዎቹ እርስ በርሳቸው ተዋውቀው፣ በጓደኝነት ቆይተውና ጉዳያቸውን ሁሉ በውጪ ጨርሰው ለጋብቻ የሚበቁበት ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት፣ ጥንዶች ጋብቻቸውን የሚፈፅሙት በቤተሰብ ይሁንታና ፈቃድ ነበር፡፡ ሴት ልጅ ለጋብቻ የምትታጨውና የምትመረጠው ባህርይዋ ታይቶም ጭምር ነበር - አንገቷን የደፋች ጨዋ መሆኗ ተመርምሮ፤ ይህንን ጨዋነቷን የምታረጋግጠው ደግሞ ህጓንና ክብሯን ጠብቃ በመገኘት ነው፡፡ ክብረ ንፅህናን እስከ ጋብቻ ዕለት ድረስ ጠብቆ አለማቆየት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እጅግ ነውር ተግባር ተደርጐ ነበር የሚቆጠረው፡፡ በሰርግ ዕለት በሴቷም ሆነ በወንዱ ቤተሰቦች ዘንድ እጅግ በጉጉት ከሚጠበቁት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሙሽራዋ ጨዋነት የሚበሰርበት የጫጉላ ምሽት ነው፡፡ እስቲ አምጣው የደሙን ሸማ
እስኪ አምጣው የደሙን ሸማ
እንድንስማማ
ተብሎ የሚቀነቀነውም ለዚሁ ነው፡፡ ይህ የሙሽራዋ ጨዋነት ማረጋገጫ ሰነድ ከሁለቱ ጥንዶች በበለጠ የወላጆችና የቤተሰብ የኩራት ምንጭ እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ይኼኛው ከዘመን ጋር እየተቀየረ ሄዶ፣ ጥንዶቹ በራሳቸው ፍላጎትና ምርጫ እየተዋወቁ በመግባባት ጋብቻቸውን በፍቃዳቸው መፈፀም ጀመሩ፡፡ ወላጆችም ለጥንዶቹ ጋብቻ ይሁንታ እንዲሰጡ ጊዜው አስገደዳቸው፡፡  
ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ አዲስ ተጋቢዎች ወደ ጋብቻ ሰተት ብለው ከመግባታቸው በፊት የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ የሚገደዱበት ሁኔታ ተከሰተ - የኤችአይቪ/ኤድስ መስፋፋትን ተከትሎ፡፡
ወንዱ ልቡ የፈቀዳትን ሴት ለማግባት ወደቤተሰቦቿ ዘንድ አማላጅ ሲልክ የመጀመርያው ጥያቄ፣ ከኤችአይቪ ነፃ መሆኑን የሚያረጋግጥ የሃኪም ማስረጃ አቅርብ የሚል ሆነ፡፡
በእርግጥ ይሄኛው ከሙሽራዋ የጨዋነት ማረጋገጫ ጋር ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም፡፡ ይሄኛው ለጋራ ደህንነት የሚወሰድ ቅድመጥንቃቄ ነው፡፡
ምናልባት የሰርግ ዘፈኖቻችንም
እስኪ አምጣው የደሙን ስሪንጅ
እስኪ አምጣው የደሙን ስሪንጅ
ትዳር ላደራጅ
ወደሚሉ ተቀይረው ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን ጋብቻ ለመፈፀም የኤችአይቪ ምርመራ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የትዳር ህይወት ሊታደጉ የሚችሉ የተለያዩ የጤና ምርመራዎች አሉ፡፡
የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አከበረኝ ወርቁ በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረጉ ጥናቶችን ጠቅሰው እንደሚናገሩት፤ ጋብቻ ለመፈፀም ያቀዱ ጥንዶች ከመጋባታቸው በፊት ማድረግ የሚገባቸው የጤና ምርመራዎች በሁለቱ ተጋቢዎች የወደፊት ህይወት ላይ እጅግ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ፡፡ በጥንዶች መሀል የተጀመረውን ትዳር በማፍረስ ረገድም እነዚህ ችግሮች ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ እነዚህ ጥንዶች ከጋብቻቸው በፊት ሊፈፅሟቸው የሚገቡ የጤና ምርመራዎች መካከል በግብረስጋ ግንኙነት ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎች፤ የሔፒታይተስ ቢ እና ሲ ቫይረስ፣ የደም ካንሰርን የሚያመጡ (ሒውማን ቲ ሴል ሊውኮትሮፒክ ቫይረስ)፣ የደም ዓይነት (Blood Type or RH factor) እና በዘር ቅልቅል ወቅት ወደ ልጁ ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎች ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ጥንዶቹ ከመጋባታቸው በፊት መመርመር ያለባቸው የጤና ችግሮችን አለመመርመር ጥንዶቹ ወደፊት የሚወልዷቸውን ልጆች በዘር ውርስ ለሚተላለፉ የልብ፣ የካንሰር፣ የስኳር በሽታዎችና መሰል ችግሮች ተጋላጭ ያደርጓቸዋል፡፡ ስለዚህም ጥንዶቹ ከጋብቻቸው ምስረታ በፊት የሚያደርጉት የጤና ምርመራ ጠቀሜታው ለሁለቱ ጥንዶች ብቻ ሳይሆን በትዳር ውስጥ ለሚፈጠሩትም ህፃናት ጭምር ነው፡፡ የሁለቱ ጥንዶች ጥምረት ከዘርመል እና አፈጣጠር አኳያ የተለያየና በልዩ ልዩ ህክምናዎች ሊስተካከል የሚችል ከሆነ ጥንዶቹ አብሮነታቸውን መቀጠል እንደሚችሉ የሚናገሩት ዶ/ሩ፤ ለዚህም እንደምሳሌ የሚያነሱት የደም ዓይነት ልዩነት (Blood Type Factors RH-or RH+መሆንን) ነው፡፡ ይህ ችግር የጤና ችግር ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ባይሆንም የሁለቱ ጥንዶች የደም አይነት መለያየት፣ ጥንዶቹ በትዳር ህይወታቸው የመውለድ ፀጋን እንዳያጣጥሙ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡
ችግሩ በህክምና እርዳታ ሊስተካከል የሚችል ችግር ቢሆንም ለህክምና የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ በርካቶች ችግሩ እንዳለባቸው እንኳን ሳያውቁ ተደጋጋሚ ውርጃን በማስተናገድ ልጅ ወልዶ መሳም ህልም ሆኖባቸው ይቀራል፡፡
ከጋብቻ በፊት በሚደረግ ምርመራ ላይ ተሳታፊ መሆን የሚገባቸው ሁለቱም ጥንዶች ሲሆኑ የምርመራውን ውጤት በተረጋጋ መንፈስና በማስተዋል ለመቀበል ዝግጁ መሆንም ከሁለቱም ጥንዶች የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ የምርመራ ውጤት የሁለቱን ጥንዶች የጋብቻ ጉዞ ሊያስቀር የሚችል ቢሆን እንኳን ሁለቱም ውጤቱን በፀጋ ለመቀበል የሚያስችል የስነ-ልቦና ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የምርመራው ውጤት ምንም ይሁን ምን በጋብቻ ሀሳባቸው ላይ ለውጥ ለማስከተል እንደማይችል የተማመኑ ጥንዶች፤ በትዳር ጉዞዋቸው ወቅት የሚደርሱትን ችግሮች ተቋቁሞ ለማለፍ እንደሚችሉ ማመን እንደሚገባቸው ዶ/ር አከበረኝ አበክረው አስገንዝበዋል፡፡
ትዳር ማለት እስከ ህይወት ፍፃሜ ድረስ ሊዘልቅ የሚችል የህይወት ጉዞ ነውና በደንብ አስቦበት መግባቱ፣ አንዴ ከገቡ በኋላ ደግሞ ኃላፊነትን ለመሸከም ዝግጁ መሆን ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡ 

Published in ዋናው ጤና
Page 2 of 13