የመሳሪያዎቹ ጠቀሜታና የጎንዮሽ ጉዳቶች
   የሰው ልጅ የሚጠቃባቸውን የተለያዩ አይነት በሽታዎች አካሉ ሳይከፈት (ያለቀዶ ጥገና) ለማየትና ለመመርመር የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከልም ሜሪና ፔሬይኩሪ በተባሉ ተመራማሪዎች የተገኘው የኤክስሬይ (ራጅ) ምርመራ መሣሪያ ቀዳሚ ሲሆን ይህ መሣሪያ አገልግሎት ላይ ከዋለ አንደ መቶ አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና እነዚህ የሰው ልጅ አካል ሳይከፈት ምርመራ ለማድረግ የሚያስችሉ መሣሪያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመኑና እየተሻሻሉ ሄደው ዛሬ ከፍተኛ መራቀቅ ላይ ደርሰዋል፡፡
እነዚህ ዘመናዊ የህክምና ምርመራ መሣሪያዎች የየራሳቸው ጠቀሜታና ጉዳቶች አላቸው። መሣሪያዎቹ የሚያደርሱት ጉዳት ከሚሰጡት ጠቀሜታ አንፃር ተመዝኖ ጥቅም ላይ ይውላሉ። የህክምና ባለሙያው ለታማሚው ምርመራውን የሚያዘው የታማሚው የጤና ሁኔታ፣ ከምርመራው ሊገኝ የሚችለውን ጠቀሜታና የታማሚውን የሚደርሱትን ችግሮች የመቋቋም አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባትና ምርመራው የሚያስከትለውን የጤና ችግር በማመዛዘን ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገራችን በስፋት ጥቅም ላይ እያዋሉ ያሉት አካልን ሳይከፍቱ ምርመራ የማድረግ ቴክኖሎጂዎች የሚያስገኙትን ጥቅሞችና ጉዳቶች በአጭር በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

አልትራ ሳውንድ (Sonography)
ተግባሩ የድምፅ ሞገድን በመጠቀም በኮምፒዩተር ምስልን ማንሳት ሲሆን ታካሚው የሰውነት አካል ላይ ፈሳሽ በማድረግ ባለሙያው በመሣሪያ በመታገዝ እያንቀሳቀሰ በሚፈልገው ቦታ ረዘም ያለ ጊዜ በመቆየት ምስሉ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ዝቅተኛ የድምጽ ሞገድን በመጠቀም የውስጥ አካላትን በዝርዝር ለማየት የሚቻል ሲሆን ከፍተኛው የድምጽ ሞገድ የቆዳ ክፍሎችን፣ ዓይንን እና የቆዳ ካንሰርን ለመለየት ያስችላል፡፡
አልትራሳውንድ ፅንስን ለመመርመር በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን የደም ቧንቧ ሁኔታን፣ ልብንና የጡት ካንሰርን ለመመርመርም ያስችላል። ቴክኖሎጂው በቀላሉ የሚገኝ፣ ውድ ያልሆነና የጐንዮሽ ጉዳቱም አነስተኛ ነው፡፡ አልትራ ሳውንድ ፅንስን ለመመርመር ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም የተደጋገመ ምርመራ ማድረጉ ግን በፅንሱ ህብር ህዋስ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡

ራጅ (X-ray Radiography)
በአብዛኛው ለአጥንት፣ ለደረት፣ ለጥርስና ለሣምባ ጤና ችግሮች ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን በአጭር የሞገድ ርዝመት ሰውነታችንን በቀላሉ ጥሶ በመግባት ምስልን ለማስቀረት (ለማየት) የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡
የራጅ የምርመራ መሳሪያ ህመም የለሽ ሲሆን፣ አጠቃቀሙ ቀላል የሆነ ቴክኖሎጂ መሆኑ፣ ውድ አለመሆኑና በተለይመ ከምርመራ በኋላ በሰውነት ውስጥ የሚቀር ጨረር አለመኖሩ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
ይህ የምርመራ ዘዴ ከሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች መካከል ወደ ሰውነታችን ውስጥ የሚዘልቀው ጨረር ኃይለኛ በመሆኑ ሣቢያ በህብረ ህዋሳቶቻችን ላይ ጉዳት ሊያስከትል መቻሉ ነው፡፡ እርጉዝ ሴቶች ይህንን የምርመራ ዘዴ መጠቀም የለባቸውም፡፡

ሲቲ ስካን (Computed Jumography) X- ray (ራጅ) መሣሪያ በዘመናዊ መልኩ ተሻሽሎ ጥቅም ላይ እንዲውል ሲደረግ የመጣ ዘመናዊ የምርመራ መሣሪያ ነው፡፡ መሣሪያው ልዩ መልዕክት ተቀባይ (Sensor) ማሽን የተገጠመለት ሲሆን ህመምተኛው በማሽኑ ውስጥ እንዲገባ ተደርጐ 360 ድግሪ በሚሽከረክሩና ብርሃን በሚፈነጥቁ መሣሪያዎች አማካይነት የታማሚውን አጠቃላይ የሰውነት ክፍል ፎቶግራፍ ለማንሣት የሚያስችል መሣሪያ ነው፡፡ መሣሪያው በአብዛኛው ለተለያዩ አይነት የካንሰር ህመሞች፣ ለደረት፣ ለአጥንት፣ ለጭንቅላትና፣ ለሆድ አካባቢ የጤና ችግሮች ምርመራ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ሲቲ ስካን ፈጣን፣ ቀላልና ህመም የሌለው የምርመራ መሣሪያ ከመሆኑም በላይ የውስጥ አካላትን ቁልጭ አድርገው የሚያሣዩ ምስሎችን ስለሚያስገኝ ሃኪሙ የበሽታውን ምንነት በቀላሉ ለማወቅ እንዲችልም ያስችለዋል፡፡
በሲቲስካን መሣሪያ ምርመራ ማድረግ የተለያዩ ጉዳቶችም አሉት፡፡ መሣሪያው ከx-ray ማሽንም ላቅ ያለ መጠን ያለው ጨረርን ወደሰውነታችን ውስጥ እንዲገባ ስለሚያደርግ በካንሰር የመጠቃት አደጋን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የምስል ጥራቱን ለማሳደግ ተብለው የሚጨመሩት ኬሚካሎች በኩላሊት ላይ ጉዳትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ሲሆን የአለርጂ ችግርም የመፍጠር አደጋ አላቸው፡፡ ይህ የመመርመሪያ መሳሪያ ለነፍሰጡር ሴትና ለአጥቢ እናቶች አይመከርም፡፡ አንዲት የምታጠባ እናት አስገዳጅ ሁኔታዎች ተፈጥረው የሲቲስካን ምርመራ ካደረገች ልጇን ቢያንስ ለሃያ አራት ሰዓታት ከማጥባት መቆጠብ ይኖርባታል፡፡
ፔቲስካን (Positron Emission Tomography)
የሰውነታችንን ውስጠኛ አካል አሠራር በምስል በማሳየት ከጤናማው አሠራር ለየት ያሉ ነገሮች መፈጠር አለመፈጠራቸውን በግልጽ ለመለየት ያስችላል፡፡
ይህ መሣሪያ  ውስጣዊ አካላችን በጉዳት ከጥቅም ውጪ ከመሆኑ በፊት ያለበትን ችግር በቅድሚያ አውቆ ለመመርመርና ወደትክክለኛ ተግባሩ ለመመለስ ይጠቅማል፡፡
በፔቲ ስካን መሳሪያ ወደሰውነታችን ውስጥ የሚገባው ጨረር ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በፅንስ ላይ አደጋን ሊያስከትል ስለሚችል ነፍሰጡሮች ምርመራውን ከማድረግ መቆጠብ አሊያም ለሃኪማቸው ስለእርግዝናቸው በቅድሚያ መናገር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኤምአርአይ (Magnetic Resonance Imaging)   
ከሬዲዮ ሞገድ ጋር ከፍተኛ አቅም ያለው ማግኔቲክ ኃይልን በመጠቀም የውስጥ አካላትን እየከፋፈለ ፎቶ (ምስል) በማውጣት ለመመርመር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በዚህ ዘመናዊ መመርመሪያ መሣሪያ በመጠቀም ሃኪሙ የታማሚውን ችግር በቀላሉ ለመለየት ይችላል፡፡ ለጭንቅላት (አንጐል) እና የአጥንት መገጣጠሚያዎችን ለመመርመር ተመራጭ መሣሪያ ነው፡፡
በዚህ መሣሪያ ምርመራ በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ማንኛውም ብረት ነክ ነገር እንዲኖር አይፈቀድም፡፡ ሰዓት፣ ጌጣጌጦች፣ የፀጉር ጌጦች፣ የብረት ዚፕ፣ ብረት ነክ መነፅሮች መያዝና ማድረግ አይቻልም፡፡ ታካሚው በማሽኑ ውስጥ በሚቆይባቸው ጊዜያት ንቅናቄ ማድረግም አይፈቀድለትም፡፡
መሣሪያው እጅግ ዘመናዊና አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጨረሮች የሌሉት በመሆኑ በተለይ ለአንጐል ምርመራ እጅግ ጠቃሚ መሣሪያ ነው። መሣሪያው የሚያወጣው ምስል ጥራት የጤና አክሉን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል ነው፡፡ ለሌሎች መሣሪያዎች የተሰወሩ ችግሮች ከኤም አር አይ ሊያመልጡ አይችሉም፡፡
ምስሉ ጥራት እንዲኖረው ለማድረግ ታስቦ የሚጨመረው ኬሚካል አንዳንድ ጊዜ አለርጂን የመፍጠር አጋጣሚዎች ይኖሩታል፡፡ ከዚያ በቀር ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የጐንዮሽ ጉዳት የለውም፡፡
መሣሪያው ብረት ነክ ነገሮችን ስለማይቀበል በሰውነታቸው ውስጥ ለተለያዩ አካላት ድጋፍ እንዲሆኑ ብረት የተገጠመላቸው ሰዎች ምርመራውን ከማድረጋቸው በፊት ስለጉዳዩ ለሃኪማቸው እንዲነግሩ ይመከራሉ፡፡
እነዚህ ዘመናዊ የህክምና መመርመሪያ መሣሪያዎች ለሃኪሙም ሆነ ለታካሚው የሚሰጡት ጠቀሜታ ከፍ ያለ ቢሆንም በመሣሪያዎቹ በተደጋጋሚ መመርመርና ያለ ባለሙያ ዕውቅናና ፈቃድ ምርመራ ማድረግ ለከፋ የጤና ችግር ሊያጋልጥ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡   

Published in ዋናው ጤና
Saturday, 21 March 2015 10:21

የፈገግታ ጥግ

የእንቅልፍ ችግር ያለበት ህመምተኛ ሃኪሙ ዘንድ ሔዶ ምርመራ ያደርግና መድኀኒት ይታዘዝለታል፡፡ ከዚያም ሃኪሙ፤ “እነዚህን መድኀኒቶች ከወሰድክ ቤትህ ተኝተህ አለምን ስትዞር ታድርና ፓሪስ ላይ ታርፋለህ” ይለዋል፡፡ በነጋታው ህመምተኛው ወደ ሃኪሙ ጋ ተመልሶ ይሄድና “ዶ/ር፤ መተኛቱን በደንብ ተኛሁ፤ ጠዋት ስነቃ ግን የተነሳሁት እዚያው ቤቴ ውስጥ ነው” ይለዋል፡፡
ሃኪሙም፤ “ምን ዓይነት ቀለም ያለው መድኀኒት ነው የሰጠሁህ?” ታማሚው “ቢጫ”
ሃኪሙም፤ “በጣም ይቅርታ፤ የሰጠሁህ የደርሶ መልሱን ክኒን ነው”

Published in ጥበብ

ውሃን መጠጣት የምግብ ስልቀጣ ሂደትን ለማፋጠንና የሰመረ ለማድረግ እንዲሁም  ቆዳን ለማጥራት፣ ድካምን ለማብረድና ትኩረት የመስጠት ችሎታን ለመጨመር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከልክ ሲያልፍ ለሞት እንደሚዳርግ የእንግሊዝ ተመራማሪዎች በቅርቡ ይፋ ያደረጉት መረጃ አመልክቷል፡፡
ከመጠን ያለፈ ውሃ መጠጣት የኩላሊትን የማጣራት ተግባር እንደሚያውክና ደማችንን በማቅጠን የሰውነታችንን የጨው ክምችት ቀንሶ ለሞት እንደሚዳርግ የጠቆመው መረጃው፤ የውሃው መጠን እጅግ ሲበዛ የአዕምሮአችን የውስጠኛው ክፍል እንዲያብጥና የአዕምሮ ስራ እንዲስተጓጎል ያደርጋል ብሏል፡፡ የደም ዝውውራችንንና ትንፋሻችንን የሚቆጣጠረው የአዕምሮአችን ክፍል በእብጠቱ ሳቢያ በሚደርስበት ጉዳት ስራው ሲስተጓጎል በትንፋሽ እጥረትና በደም ዝውውር መዛባት ምክንያት ለህልፈት ልናደርግ እንደምንችል መረጃው አመልክቷል፡፡
አንድ ሰው በየሁለት ሰዓቱ ከአንድ ጊዜ በላይ ሽንቱን ለመሽናት ወደመፀዳጃ ቤት ከተመላለሰና የሽንቱ ቀለም ንፁህ ውሃ የሚመስል ከሆነ፣ የጠጣው ውሃ ከመጠን ማለፉን እንደሚያመለክትም ተማራማሪዎቹ ይፋ ያደረጉት መረጃ ይጠቁማል፡፡

Published in ዋናው ጤና

   ጉንፋን፣ ሳልና ብሮንካይትስ እየተመላለሰ ያሰቃያችኋል? በእነዚህ የጤና ችግሮች በተደጋጋሚ የምትጠቁ ከሆነ ፋርማሲ መሄድ ሳያስፈልጋችሁ ወጥ ቤት ብቻ ጎራ ብላችሁ ራሳችሁን ልትፈውሱ ትችላላችሁ፡፡
በርበሬ፣ ሚጥሚጣ፣ ቃሪያ… እንደ ሰናፍጭ ያሉ የመሰንፈጥ ባህርይ ያላቸው ምግቦች፡- ኮምጣጤና ነጭ ሽንኩርት በሳምባ ውስጥ ያሉ የአየር ቧንቧዎችን በመክፈት አየር ወደ ሳምባ እንደ ልብ እንዲገባና እንዲወጣ ወይም በዚህ ችግር ምክንያት የሚፈጠረውን ሳል የማቆም ኃይል እንዳላቸው ተረጋግጧል፡፡
እንደ ቃሪያ ያሉ የማቃጠል ባህርይ ያላቸው ምግቦችን በምንመገብበት ወቅት አፋችንን የሚያቃጥለን ካፕሲካን (capsican) የተባለው ኬሚካል ጋውፊሲን (Guaifenesien) ከተባለው የመተንፈሻ አካላት መድኀኒት ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡
በብሮንካይትስ ወይንም በጉንፋን ምክንያት ጉሮሮአችሁን መከርከር ሲጀምራችሁ ወይም ጉንፋን ሊይዛችሁ ከመሰላችሁ 3 ቀይም 4 ፍሬ ነጭ ሽንኩርት ልጣችሁ በውሃ ዋጡት፡፡ ነጭ ሽንኩርት የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን በተለይም ጉንፋንና ብሮንካይትስ የሚያሲዙ ቫይረሶችን 95 በመቶ የመግደል አቅም አለው፡፡
በሾርባ ውስጥ ቃሪያ፣ ሚጥሚጣና ነጭ ሽንኩርትን ጨምሮ መመገብ፤ ትኩስ በዝንጅብል የተፈላ ሻይ ላይ ማር ጨምሮ መጠጣት በጉንፋን የመያዝ ዕድልን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡

Published in ዋናው ጤና
  • “ገዢው ፓርቲ ሰለቸኝ” የሚል ራሱን በፍጥነት ከድህነት ያውጣ!
  • “ኢህአዴግ ሥልጣን የሚፈልገው እኛን ከድህነት ለማውጣት ነው”

   ከቅርብ ጊዜ  ወዲህ አውራ፣ ገናና፣ ህዝባዊ፣ ልማታዊ፣ አብዮታዊ፣ ድሃ ተኮር፣… ወዘተ የሚሉ ቅፅሎች እንደ ጉድ የተጫኑለት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ የሥልጣን መንበሩን ከተቆናጠጠ ይኸው ሩብ ክ/ዘመን ሊያስቆጥር ነው! (በገዢዎች ሳይሆን በተገዢዎች የጊዜ ሰሌዳ ማለቴ ነው!) እኔ የምፈራለት ግን ምን መሰላችሁ? ዕድሜው እየጎለመሰ በሄደ ቁጥር የሚያከብራቸው በዓላት እየበረከቱ ስለሚመጡ ከልማታዊነት እንዳያቦዝነው ነው፡፡ (ግንቦት 20፣ የህወሃት 40ኛ ዓመት፣--የኢህአዴግ የብር ኢዮቤልዩ…ወዘተ!) በዓላት እኮ ለኒዮሊበራሎች እንጂ ለልማታዊ ፓርቲዎች ብዙም አይመቹም፡፡
በነገራችን ላይ --- ኢህአዴግ ሌላ ተጨማሪ 30 እና 40 ዓመታት አገሪቱን የመግዛት ህልም እንዳለው በየአጋጣሚው እየገለጸ ነው፡፡ (ኢዴፓ “መመኘት መብቱ ነው” ያለው መሰለኝ፡፡) እኔ ደግሞ “የያዝከውን ያበርክትልህ” ልለው አስቤ ነበር፡፡ (ሥልጣን ግን መቅኖ የለውም፤የዘንድሮ 100 ብር በሉት!) እውነቱን ለመናገር---ኢህአዴግ ስልጣኑን ለምን ማራዘም እንደፈለገ በቅጡ ባላውቅ ኖሮ ጨሼም አላባራ ነበር፡፡ (መረጃ ፈውስ ነው!)
እናላችሁ--ኢህአዴግ ይህችን 30 እና 40 ዓመት የሚፈልጋት (በልማታዊ መንግስት አቆጣጠር 3 ዓመት ብትሆን ነው!)  ለግል ጉዳዩ ሳይሆን የህዝቡን ምቾት ለማደላደል ብቻ ነው (ከተጠራጠራችሁ በውሸት detecetor ፈትሹኝ ብሏል!) እንደውም እኮ---ህዝቡን ከድህነት አረንቋ አውጥቼ ሰው ካላደረግሁት፣ እንቅልፍ በአይኔ አይዞርም ብሎ ተፈጥሟል አሉ፡፡ (እኛንም እንቅልፍ ሊነሳን ነዋ!)
አንዳንድ “ፍንዳታ ፖለቲከኞች” ግን እቺን ለ30 ዓመት ሥልጣን የማስረዘም ጉዳይ ፈጽሞ አልወደዷትም፡፡ ምን እንዳሉ ታውቃላችሁ? “ኢህአዴግ ሌላ 50 ዓመት ከጨቀጨቀንማ ላይፍ ቦሪንግ ይሆናል!” (ግዴለም ሲበስሉ ይረዱታል!) እኔን ከሁሉ ያስገረመኝ ግን ኢህአዴግን ለመንቀፍ ሁሌም ቢላቸውን ስለው የሚጠብቁ አቃቂረኞች አሉት የተባለው ነው፤ “ኢህዴግ ሞናርኪ ሊሆን ነው!” (ተጨማሪ 30 ወይም 40 ዓመት መጠየቅ ንጉሳዊ አገዛዝ ያሰኛል?) እነዚህን እኮ ነው ኢህአዴግ “የሰፊው ህዝብ ጠላቶች---”የሚላቸው! (የእኔ ጠላት ሊላቸው አይችልማ!)
ይሄውላችሁ----እኔ ግን አንድ ሁነኛ መላ አለኝ፡፡ “ኢህአዴግ ሰለቸኝ” የሚል ወገን ሁሉ ራሱን በብርሃን ፍጥነት (ብርሃን እንደ ልብ ባይገኝም!) ከድህነት መንጭቆ ያውጣ! ምክንያቱም የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች “ሚድል ክላስ” ከተፈጠረ በኋላ ፓርቲው ይከስማል ብለዋል፡፡ (በሞጃ መራሽ ፓርቲ ይተካል ማለት ነው!) አንዳንድ ተቃዋሚዎች ግን በኢህአዴግ ጥያቄ ከመቃጠላቸው የተነሳ “ወራጅ አለ!” እያሉ ነው፡፡ ለመሆኑ ማነው ኢህአዴግን “የድህነት ነፃ አውጪ ያደረገው” ሲሉም አበክረው ይጠይቃሉ፡፡ (ይሄን እንኳን ራሱ ቢመልሰው ይሻላል!)
የሆኖ ሆኖ እንዳለመው ከሆነለት፣ኢህአዴግ ጦቢያን ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ በመግዛት ሪከርድ ይሰብራል ማለት ነው፡፡ ይሄን ሃሳብ ለሚነቅፉ ወገኖች ሁሌም የሚጠቅሰው ደግሞ ጃፓንን ነው - (በምርጫ ክርክሩም ደረቱን ነፍቶ እየተናገረ  ነው!) ጃፓን ዛሬ ያለችበት ደረጃ የደረሰችው ለ100 ዓመት በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ብቻ እየተመራች ነው በማለት። እኔ የምለው----የሥልጣን ትራንስፎርሜሽኑ ሲጀመር (የ30 እና 40 ዓመቱን ማለቴ ነው!) ባሎት (ምርጫ) ከእነአካቴው    ይቀራል ማለት ነው? (ለህዝብ ከበጀ ለምን ጥንቅር አይልም!)
በነገራችሁ ላይ በዛሬው የፖለቲካ በፈገግታ ወጋችን የምናስተናግደው ከህዝብ የቀረበ አቤቱታ ነው፡፡ (እንዳቅሚቲ’ኮ የህዝብ አምድ ነው!) እናላችሁ … አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ኢህአዴግ ሥልጣን ከተቆናጠጠ ጀምሮ አሳይቶ የነሳን “በረከቶች” ተቆጥረው አያልቁም … በማለት ምሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እስካሁን አሳይቶ ያልነሳን ነገር ቢኖር --- “አብዮታዊ ዲሞክራሲ”ን  ብቻ ነው ብለዋል - ፍርጥም ብለው፡፡ (ርዕዮተ ዓለሙን ማለታቸው ነው!) በነገራችን ላይ አሳይቶ መንሳትና አይቶ ማጣት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው!  (አንድዬ ከሁለቱም ይሰውረን!)
አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ኢህአዴግ አሳይቶ ነሳን ከሚሉት ውስጥ የግል ጋዜጦች መመናመንን ይጠቅሳሉ፡፡ ከምርጫ 97 በፊት የነበሩትን በመቶዎች የሚቆጠሩ የነፃው ፕሬስ ትሩፋቶች፣ ከአሁኑ ዘመን በጣት የሚቆጠሩ የፕሬስ ውጤቶች ጋር በማነፃፀር ያጡትን እያሰሉ በቁጭት ይንገበገባሉ፡፡ (በእንስራ አሳይቶ በጣሳ መስጠት ብለውታል!) እንደ ዘንድሮ “የምርጫ ታዛቢው ራሱ ህዝቡ ነው!” ከመባሉ በፊት በየአምስት ዓመቱ ባህር ተሻግረው የሚመጡትን ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች (በተለይ የአውሮፓ ህብረት፣ አፍሪካ ህብረትና የካርተር ፋውንዴሽን) በምልሰት ወደ ኋላ ተጉዘው በማስታወስም የተቆጩ አልጠፉም፤አውራው ፓርቲ እያሳየ የነሳን አበዛዙ… በሚል፡፡ “ታዛቢዎቹ ምርጫውን ባይታዘቡ እንኳ ለአገር ገፅ ግንባታ ሲባል መጋበዝ ነበረባቸው ባይ ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በዘንድሮ ምርጫ የማይታዘበው እንደተባለው በአቅም እጥረት ሳይሆን አንድም ባለ መጋበዙ አንድም ደግሞ መንግስት ህብረቱ የሚያቀርበውን የምርጫ ሪፖርት ስለማይቀበል እንደሆነ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡)
አምና መንግስት በመሰረተባቸው ክስ የተዘጉትን ከ6 የማያንሱ የግል መፅሄቶችና የሚዲያ ተቋማት እንዲሁም  የተሰደዱ ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች--- የምርጫ መቃረብ ምልክቶች ናቸው ሲሉ ዓለምአቀፍ የፕሬስ መብት ተሟጋቾች ተችተዋል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ግን ከምርጫም ጋር ሳይነካኩ በቀጥታ ከራሳቸው መብት ጋር ነው ያያዙት፡፡ መረጃ የማግኘትና ሃሳባችንን በነጻ የመግለፅ መብታችንን አሳይቶ ነሳን (የፈረደበት ኢህአዴግን ነው!) የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ የጋዜጦች ቁጥር ከ100ዎች ወደ አስሮች ሲያሽቆለቁሉ ---የባሰ አታምጣ ብለን በጸጋ መቀበላችን ባዶአችንን አስቀርቶናል ሲሉ ክፉኛ ይቆጫሉ፡፡ (የፕሬስ አብዮት አስበው ነበር እንዴ?)
ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ስሟ በበጎ እየተገነባ የነበረችውን አገርም በአንዴ ጥላሸት በመቀባት የአገር ገፅ ግንባታውን አሳይቶ ነሳን ብለዋል፤ በምሬት። ጦቢያ በሰብዓዊ መብት አያያዝና በፕሬስ ነፃነት አጠባበቅ መቼም ቢሆን አመርቂ ውጤት አስመዝግባ ባታውቅም እንዳሁኑ ግን ውጤቷ በሁለት ዲጂት አሽቆልቁሎ አያውቅም ይላሉ፤ አቤቱታ አቅራቢዎቹ፡፡ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰርና ከአገር በማሰደድ ከአፍሪካ ተሽላ የተገኘችው በአንደኝነት ደረጃ ከተቀመጠችው ኤርትራ ብቻ ነው የሚሉት ምሬተኞቹ፤ ይሄም የአሳይቶ መንሳት ፍሬ ነው ብለዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በመልካም አስተዳደርና በሙስና በኩል ምንም አሳይቶ የነሳን ነገር ስለሌለ ተመስጌን ነው ይላሉ - የነበረው ችግር ተባብሶ ከመቀጠሉ ውጭ የተፈጠረ ነገር እንደሌለ በመጥቀስ። በ97 ምርጫ ማግስት በተቃዋሚዎች ተይዘው የነበሩት የፓርላማ መቀመጫዎች ተመናምነው አንድ ለመድሃኒት ብቻ መቅረቱንም አሳይቶ  የመንሳት ትሩፋት እንደሆነ አምርረው ይገልፃሉ፡፡ (ኢህአዴግ እንግዲህ ወንበሩን አይለቅላቸው!) በመጨረሻም እንደ አይቶ ማጣት ክፉ እርግማን የለም ሲሉ ጦቢያ ዳግመኛ አይታ እንዳታጣ እንፀልያለን ብለዋል - በአንድ ቃል!!
እኔ ግን ኢህአዴግ እነዚያን ሁሉ “በረከቶች” አሳይቶ የነሳን ሆን ብሎ አይመስለኝም፡፡ (ማንን ደስ ይበለው ብሎ?!)  አያችሁ … ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊት በአልባንያ ሶሻሊዝም የተጠመቀ ማርክሲስታዊ ድርጅት ነበር፡፡ ከዚያም ዓለምን ለመምሰል “ነጭ ካፒታሊዝም”ን እንደሚከተል ሲናገር ቆየ (ቢያንስ በኢኮኖሚው ዘርፍ!) ወደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የተሸጋገረው በኋላ ነው፡፡
አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲ (ኒዮ-ሌኒኒስት የፖለቲካ ሞዴል ነው!) ከሌኒኒዝም፣ ከማርክሲዝም፣ ከማኦይዝምና ከሊበራሊዝም ውጭ የሚንቀሳቀስ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ አስቡት…ለራሱም ለኢህአዴግ እንኳን እንዴት እንግዳ የሆነ ርዕዮተ ዓለም እንደነበር! እናላችሁ … ምን እጠረጥራለሁ መሰላችሁ? (መረጃ ከሌለ መጠርጠር መብት ነው!) ገዢው ፓርቲው ሳያውቀው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሚፈቅደው ውጭ ብዙ “ነፃነቶች”ን ሲያሽረን ከርሟል። ከርዕዮተ ዓለሙ ጋር በቅጡ ሲተዋወቅ ደግሞ ነገሮችን መስመር ማስያዝ ነበረበት፡፡ “ኢህአዴግ  እያሳየ የነሳን በረከቶች አበዛዛቸው---” የሚለው አቤቱታ የተወለደውም በዚህ ሂደት ይመስለኛል። (“አይቶ ማጣት የወለደው----የእንትን ሠራዊት” የሚል እንዳይመጣ ፍሩልኝ!)
በእርግጥ ኢህአዴግ ከነቃም በኋላ የአብዮታዊ ዲሞክራሲን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንጂ ፖለቲካዊ ነገሩን በግልፅ አልነገረንም፡፡ (ፈርቶ ይሆናላ!) አብዮታዊ ዲሞክራሲ፤ መንግስት በተገደበ መልኩ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት ርዕዮተ ዓለም መሆኑን በተደጋጋሚ ነግሮናል (ኧረ በተግባርም አሳይቶናል!) ያልተነገረን የፖለቲካው ነገር ነበር፡፡ እሱም ቢሆን ግን የሮኬት ሳይንስ አይደለም፡፡ ከእስከዛሬው የልማታዊ መንግስታችን ተግባራዊ ተመክሮ ተነስተን እንዲህ ነው ማለት አያቅተንም፡፡ እናላችሁ ---- አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሲያስፈልግ መንግስት ያለ ገደብ ፖለቲካው ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት የዲሞክራሲ ስርዓት ማለት ነው፡፡ (ከኖርነው ተነስተን ማለት ነው!)
እዚህ ጋ ግን አንድ እውነታ መዘንጋት የለብንም። መንግስት ኢኮኖሚው ውስጥ በተገደበ መልኩ ጣልቃ የሚገባውም ሆነ ፖለቲካው ውስጥ ያለ ገደብ ዘው የሚለው የሰፊውን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል ነው፡፡ (ኢህአዴግ ከህዝብ የወጣ፣ በህዝብ የተፈተነ፣ ህዝባዊ ፓርቲ መሆኑን እንዳትዘነጉ!) በ97 ምርጫ ማግስት ምን አደረገ? አብዮታዊ ዲሞክራሲ በሚፈቅድለት መሠረት፤ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ገደብ ጣልቃ በመግባት፣ ለህዝብ አይበጁም ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ድራሻቸውን አጠፋ (ያኔ የታገደው ሰላማዊ ሰልፍ ከ8 ዓመት በኋላ ተፈቀደ!)
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዋናው መሠረታዊ ነገር ምን መሰላችሁ? ተጀምሮ እስኪያልቅ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አድራጊ ፈጣሪው መንግስት ነው፡፡  እናላችሁ … የግል ፕሬሱ ፅንፈኝነቱን ያለቅጥ አብዝቶት የፖለቲካ ሥርዓቱን ሲያዛባ መንግስት ዘው ብሎ ክስ በመመስረት … ከአንድ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መንግስት የሚጠበቅበትን ተወጣ፡፡ (የሚዲያ ተቋማቱ ተዘጉ፤ ጋዜጠኞች ከአገር ተሰደዱ!) ተቃዋሚ ፓርቲዎች የውስጥ ችግራቸውን መፍታት ሲሳናቸው ጣልቃ ገብቶ መፍትሄ ባጃቸው፡፡ ሌሎችም በምርጫው ሂደት የተከሰቱ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ (ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል እንጂ!)
የመንግስት ጣልቃገብነት በኢኮኖሚው (በተገደበ መልኩ!)… የመንግስት ጣልቃገብነት በፖለቲካው … የመንግስት ጣልቃገብነት በፕሬስ ነፃነት … የመንግስት ጣልቃገብነት በዲሞክራሲው … የመንግስት ጣልቃገብነት በሰላማዊ ሰልፍ… የመንግስት ጣልቃ ገብነት በፓርቲዎች እንቅስቃሴ … ወዘተ … ያለ ገደብ ይፈቅዳል - አብዮታዊ ዲሞክራሲ!! ይሄ ሁሉ ጣልቃ ገብነት ደግሞ መብት ለመግፈፍ ወይም ነፃነት ለማፈን አይደለም፡፡ የህዝቡን ጥቅም የበለጠ ለማስጠበቅ ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የህዝብ አለኝታ ነው! (ወይም ነኝ ይላል!)


“የዛምቢያን ባህል ሳልረሳ የፖላንድን ባህል ተምሬአለሁ”

በትውልድ ዛምቢያዊ የሆኑት ፕሮፌሰር ኪለን ሙንያማ፤ የፖላንድ የፓርላማ አባል ሲሆኑ በተለያዩ ጊዜያት በፖላንድ በተካሄዱ ምርጫዎች ተወዳድረው በከፍተኛ ድምፅ በማሸነፍ ለመመረጥ በቅተዋል፡፡ የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እዚያው ፖላንድ የተከታተሉ ሲሆን በኢኮኖሚክስ የማስትሬትና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከፐዝናን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡ ፕሮፌሰን ኪለን ባለፈው ሳምንት ከኢትዮ - ፖላንድ የፓርላማ ቡድን ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት አድርገዋል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ ከፕሮፌሰሩ ጋር በነበራት ቆይታ በጉብኝታቸው፣ በፖለቲካ ህይወታቸው፣ በአውሮፓ የኢኮኖሚ ቀውስና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

     የኢትዮጵያ ጉብኝታችሁ በምን ላይ ያተኮረ ነው?
ጉብኝታችን ለኢትዮ-ፖላንድ የፓርላማ ቡድን በተደረገው ግብዣ መነሻነት የተከናወነ ነው፡፡ ግብዣው የተላከው በ2013 ዓ.ም ሲሆን ለጉዞው የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት አሁን ልንመጣ ችለናል፡፡ በጉብኝቱ የሚሳተፈው የልኡካን ቡድን በፓርላማ አባላቱ ብቻ ከሚወሰን ከኢትዮጵውያን ጋር በትብብር ለመስራት የሚፈልጉ   የተለያዩ የፖላንድ የቢዝነስ ኩባንያዎችን እንዲያካትት ባደረግነው ጥረት ስድስት ትላልቅ ኩባንያዎችን ይዘን ነው የመጣነው፡፡ የአፍሪካ ፖላንድ የንግድ ምክር ቤት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የሚፈልጉትን ኩባንያዎች በማደራጀት በኩል አግዞናል፡፡ ስለዚህ የጉብኝቱ አላማ ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም ነው ማለት ይቻላል፡፡
የኢትዮ - ፖላንድ የፓርላማ ቡድን ዓላማ ምንድን ነው?
ፓርላማዎች የሚመሳሰሉባቸውና የሚለያዩባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የፖላንድ ፓርላማ የራሱ አወቃቀር አለው፡፡ ፓርላማው የተለያዩ ኮሚቴዎችና የፓርላማ ቡድኖች አሉት፡፡ የፓርላማው ቡድኖች ከተለያዩ አገሮች ፓርላማዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይሰራሉ፡፡ የፓርላማ አባላቱም የሚፈልጉትን አገር የፓርላማ ቡድን ይቀላቀላሉ፡፡ የቡድኖቹ አላማ በአገሮቹ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ላይ ያለመ ነው፡፡ ፓርላማችን ከአስራ አምስት የአፍሪካ አገሮች ጋር የፓርላማ ቡድን ግንኙነት አለው፡፡ የኢትዮ-ፖላንድ የፓርላማ ቡድንም አንዱ ነው፡፡ እኔ የኢትዮ-ፖላንድ፣ የዛምቢያ - ፖላንድ እና የኬኒያ - ፖላንድ የፓርላማ ቡድኖችን በሊቀመንበርነት እመራለሁ፡፡ በሌሎች በተለይ ከአፍሪካ ጋር የተገናኙና በፖላንድ አሜሪካን ቡድን፣ በብሪቲሽ ፖላንድ፣ በፖርቹጋል ፖላንድ የፓርላማ ቡድኖች ውስጥ በአባልነት እሳተፋለሁ። የፓርላማ ቡድኖቹ  ሊቀመንበር ወይም አባል ከሆኑባቸው አገሮች የሚመጡ ልኡካንን ተቀብሎ ያነጋግራል፣ በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ይሰራል፡፡ የኢትዮ ፖላንድ የፓርላማ ቡድን አላማም ይኸው ነው፡፡
በብረታብረትና ኢንጂኒየሪንግ ኮርፖሬሽን ያደረጋችሁት ጉብኝት አላማ ምን ነበር?
አብረውን የመጡት ኩባንያዎች ስለ ስራቸው አስተዋውቀዋል፡፡ የድርጅታቸውን የሥራ ታሪክና በትብብር መስራት የሚፈልጉባቸውን መስኮችም ለብረታብረትና ኢንጂኒየሪንግ ኮርፖሬሽን ሰጥተዋል፡፡ አንዳንዶቹ መስኮች ኮርፖሬሽኑ  በጣም ትብብር የሚፈልግባቸው እንደሆኑ ተገንዝበናል፡፡ ጉብኝታችንና የተደረጉት ውይይቶች ጥሩ ውጤት ያመጣሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ አብረውን የመጡት ኩባንያዎች የብረታብረትና ኢንጂኒየሪንግ ኮርፖሬሽን ከሚሰራቸው ስራዎች ጋር የሚገናኝ ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡
እንዴት ነው ወደ ፖለቲካው የገቡት? አፍሪካዊ ሆነው እንዴት የፖላንድ የፓርላማ አባል ለመሆን ቻሉ?
ሁሉም ነገር የሆነው የፖላንድ ዜግነት ካገኘሁ በኋላ ነው፡፡ በመጀመሪያ ወደ ፖላንድ የሄድኩት እ.ኤ.አ በ1981 ዓ.ም ለትምህርት ነበር። ከኔ ጋር አራት ዛምቢያውያን ስንሆን፣ አስራ አራት ኢትዮጵያውያንም አብረውን ነበሩ፡፡ አንድ አመት የቋንቋ ኮርስ ከወሰድኩ በኋላ  ትምህርቴን በመቀጠል በ1987 ነበር ያጠናቀቅሁት፡፡ በነገራችን ላይ ሁላችንም አገራችንን ስንለቅ የመጀመሪያ ዲግሪያችንን ይዘን ለመመለስ በሚል ነበር፡፡ ወደ አገራችን የተመለስነው ግን የማስተርስ ዲግሪያችንን ሰርተን ነበር፡፡ ትምህርቴን እንደጨረስኩ እዚያው ፖላንድ ስልጠና የማግኘት እድል ስለተሰጠኝ ስልጠናዬን ጨርሼ ነው ወደ ዛምቢያ የተመለስኩት። ለሶስት ወራት ያህል በዛምቢያ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ከሰራሁ በኋላ እንደገና የዶክትሬት ዲግሪዬን ለመስራት እዚያው ፖላንድ ስኮላርሺፕ በማግኘቴ፣ በ1988 ዓ.ም ወደዚያው ሄድኩ፡
ኮሙኒዝም እየከሰመ የነበረበት ወቅት ነው። በዚህ የተነሳ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታዎች እየተለወጡ ነበር፡፡ በመጨረሻም ኮሙኒዝም ሙሉ በሙሉ ሲወድቅ በሰዎች ህይወት ላይ ለውጥ መጣ። የዶክትሬት ዲግሪ የመመረቂያ ፅሁፌን ከማቅረቤ በፊት የዩኒቨርሲቲ መምህር ሆኜ ተመደብኩ፡፡ በ1999 ዓ.ም ደግሞ የፖላንድ ዜግነት አገኘሁ፡፡
ይኼኔ ነው ወደ ፖለቲካው የገቡት?
በ2002 ዓ.ም የአካባቢ ምርጫ ይደረግ ነበር፡፡ የዲስትሪክት (አውራጃ) ሀላፊው ለዲስትሪክት ምክር ቤቱ እጩ ሆኜ እንድቀርብ ጥያቄ ሲያቀርብልኝ በጣም ነበር ያስገረመኝ፡፡ ፖለቲካ ውስጥ የመግባት ምንም አይነት ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ እዚያ ብዙ አመታትን ያሳለፍኩ ብሆንም ምርጫ ተወዳድሬ አሸንፋለሁ ብዬም አስቤ አላውቅም፡፡ ለሃላፊው  “ምርጫ እኮ የመራጮች ድምፅ ነው” ስለው፤ “ምርጫውን ተወዳድረህ ማሸነፍ ትችላለህ፤ ስለዚህ መወዳደር አለብህ” ብሎ ገፋፋኝ፡፡ እንግዲህ የሚሆነውን እናያለን ብዬው ተስማማሁ፡፡ ምንም አይነት የምረጡኝ ቅስቀሳ አላደረግሁም፣ ድምፅ የማገኝ ከሆነ የራሴንና የባለቤቴን ሁለት ድምፅ ብቻ እንደሚሆን በመገመት ወደ ምርጫው ገባሁ። ግምቴ ግን በጣም የተሳሳተ ነበር፤ አብላጫ ድምፅ በማግኘት ምርጫውን አሸነፍኩ፡፡ ያልጠበቅሁት ውጤት ስለነበር በጣም አስገረመኝም አስደሰተኝም።
ከዚያ በኋላ መራጮች ከኔ የሚፈልጉትን መስጠት እችላለሁ ወይ የሚለው ነገር የሚያሳስበኝ ሰው ሆንኩ፡፡ የተመረጥኩት ለአራት አመት ስለነበር የስራ ዘመኑ ሲያበቃ፣ ራሴን ለአውራጃ ምክር ቤት  ሳይሆን ከሱ ከፍ ወዳለው የክልል ፓርላማ እጩ አድርጌ አቀረብኩ፡፡ የክልል ፓርላማው ተመራጭ ለመሆን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ “ሲቪክ ፕላትፎርም” የተባለውን የሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ተቀላቀልኩና በ2006 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ አሸንፌ የክልል ፓርላማ ገባሁ፡፡ ከአራት  አመት በኋላ እንደገና በክልል ምርጫ አሸነፍኩ፡፡ በ2011 ዓ.ም በተደረገው አገራዊ የፓርላማ ምርጫ ፓርቲዬ እንድወዳደር እጩ አድርጎ ሲያቀርበኝ “ተወዳድሮ ማሸነፍ ይችላል ብላችሁ ካመናችሁ እወዳደራለሁ” ብዬ ተስማማሁ፡፡ የፖላንድ የፓርላማ ስርአት ተመጣጣኝ ውክልና (ፕሮፖርሽናል ሪፕረሰንቴሽን) ስለሆነ እኔ በምወዳደርበት የምርጫ ጣቢያ አራት የኔን የፓርቲ ወኪሎች ጨምሮ ዘጠኝ ተወዳዳሪዎች ነበርን፡፡ ከኔ ፓርቲ አባላት ውስጥ እኔ በማሸነፌ ፓርላማውን ተቀላቀልኩ፡፡
መራጩ ህዝብ ከእርስዎ የሚፈልገውን አሟልቻለሁ ብለው ያስባሉ?
ይህን ሊመልሱ የሚችሉት የመረጡኝ ሰዎች ናቸው፡፡ በመጪው ጥቅምት ወር በሚካሄደው ምርጫ ላይም ለመወዳደር አስቤያለሁ፡፡ ያኔ የማገኘውን ድምፅ አይቼ መናገር እችላለሁ፡፡ በእኔ በኩል ለተመረጥኩበት ቦታ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ማድረግ የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ ባይ ነኝ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ  ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስ እንዴት ይገልፁታል?
አውሮፓን በአራት መክፈል እንችላለን፡፡  38 አገሮችን የሚያካትተው የአውሮፓ ህብረት፣ 19 አገሮችን ያቀፈው ዩሮላንድ የሚባለው የአውሮፓ ሞኒተሪ ህብረት፣ የአውሮፓ የነፃ ገበያ ቀጠና አገሮች እና የአውሮፓ ህብረት አገሮች ያልሆኑት የምስራቅ አውሮፓ አገሮች እነ ራሺያ፣ ዩክሬይን፣ቤላሩስ፣ ሰርቢያ፣ሞንቴኔግሮ፣ ቦስኒያሄርዞጎቪኒያ  የሚገኙበት ምድብ አለ፡፡ ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ በዋነኛነት የማተኩረው ዩሮን በመገበያያ ገንዘብ በሚጠቀሙ  ዩሮላንድ ወይም የአውሮፓ ሞኒተሪ ህብረት በሚባለው ምድብ ላይ ባሉ አገሮች ነው። የኢኮኖሚ ቀውሱ የተፈጠረው ገንዘብ በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር በተያያዘ ሳይሆን በአባል አገሮቹ በተለይ በግሪክ፣ ስፔን ፣ ፖርቹጋል፣ ጣሊያንና  አየርላንድ ውስጥ በተከሰቱ ውጣውረዶች ሳቢያ ነው፡ አገራቱ የኢኮኖሚ እድገታቸው መሻሻልን ቢያሳይም አሁንም ችግሮች አሉባቸው፡፡  ለምሳሌ ግሪክ  የበጀት እጥረትና ከፍተኛ የዕዳ ጫና አለባት፡፡ የነዚህ አገሮች እጣ ፈንታ የሚወሰነው በዩሮ ጥንካሬ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የዩሮ የመግዛት አቅም ማጣት ይበልጥ ችግሩን ያወሳስበዋል፡፡ አንድ ሰው ከሰውነት ክፍሉ የተጎዳ ቦታ ካለ፣ ያንን ክፍል መቆጣጠር መከታተል ይጠበቅበታል፡ ግሪክ በአሁኑ ወቅት ልዩ ክትትል የሚያስፈልጋት የህብረቱ አገር ሆናለች። አዲሱ የግሪክ መንግስት አገሪቱ በህብረቱ ውስጥ የሚጠበቅባትን ግዴታ ለመፈፀም ጊዜ እንዲሰጣት እየተደራደረ ነው፡፡ ከዩሮላንድ ውጪ ያሉ አገሮችን ስናይ ለምሳሌ ፖላንድ፣ ሀንጋሪ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ስዊድንና ብሪቴይን አፈፃፀማቸው የከፋ አይደለም። እኛን (ፖላንድን) ብታይ እያደግን ነው፡፡
የአውሮፓ ህብረትና አይኤምኤፍ፤  ስፔይንና  ግሪክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ብድር እንዲያገኙ ቢጥሩም በተለይ በግሪክ ስልጣን የያዘው አክራሪው ግራ ፓርቲ ለማሻሻያዎቹ ዝግጁ አይደለም፡፡ አይኤምኤፍና የአውሮፓ ህብረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ብድር እንዲለቁ ይፈልጋል። በፍላጐቱ መሰረት ምላሽ ቢያገኝ ዕዳውን የሚከፍለው ማነው?
አገሮቹ ኢኮኖሚያቸው የሚያገግምበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው፡፡ የገንዘብ ብድርን በተመለከተ ቅድመ ሁኔታ አስፈላጊ ነው፡፡ የግሪክን ሁኔታ ስናይ አክራሪነት ብቸኛ መፍትሄ አይደለም፤ ለስለስ ማለት ያስፈልጋል፡፡ የአለምአቀፍ የገንዘብ ተቋም አባል ለመሆን ተቋሙ ለሚያስቀምጠው ህግ ተገዢ መሆን ይገባል፡፡ ዕዳውን ማነው የሚከፍለው ላልሽው… ከፋዮቹ ዜጎች ናቸው፡፡ እንግዲህ ግሪክ አትሸጥ፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ታክስ በመጣልና በመሳሰሉት መንገዶች ዜጎች ዕዳውን ይከፍላሉ፡፡ አፍሪካ እንደ አህጉር 300 ቢሊዮን ዩሮ ቢሰጣት ምን ያህል መሰረተ ልማት ሊገነባ እንደሚችል መገመት አያቅትም፡፡ ግሪክ 10 ሚሊዮን የማይሞላ ህዝብ ይዛ ይህን ያህል ገንዘብ ነው የጠየቀችው፡፡  ከዚህ አንፃር በአገሪቱ ጠንካራ የሆነ የሀላፊነት ስሜት፣  የተጠያቂነት ስርአት ሊኖር ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ፖለቲካ እየተለወጠ ነው፡ አክራሪ የግራ ፓርቲዎች በግሪክና በስፔይን እንዲሁም አክራሪ የቀኝ ኃይሎች በፈረንሳይና በእንግሊዝ፤ ብሔርተኞች ደግሞ በሀንጋሪ እየተጠናከሩና ምርጫዎችንም እያሸነፉ ነው፡፡ የዚህ አንደምታው ምንድን ነው?
አክራሪ ሀይሎች በአውሮፓ እየተጠናከሩ የመምጣታቸው ጉዳይ ምቾት የሚሰጥ አይደለም። ለዚህ ሁኔታ መከሰት  ብዙ ምክንያቶች አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ አውሮፓ ለአውሮፓውያን ብቻ እንድትሆን እንዲሁም የአውሮፓ የመገበያያ ገንዘብ አውሮፓ ውስጥ ብቻ በስራ ላይ እንዲውል የሚፈልጉ ወገኖች አሉ፡፡  አውሮፓውያን ብቻ ሳይሆኑ ከተለያዩ ባህሎች እንዲሁም  ከሀይማኖት ጋር በተያያዘ ደስተኞች ያልሆኑ  ወገኖችም አሉ። በኔ አስተያየት አለም አንድ እየሆነ በመጣበት በግሎባላይዜሽን ዘመን የራሴ በሚል ተከልሎ መኖር አይቻልም፡፡ አሁን የሚያስፈልገው የራስን ከልሎ መያዝ ወይም ሌሎችን አግልሎ መኖር ሳይሆን ውህደት ነው፡፡
እኔ “ዘ ፓርላሜንታሪ አሴምብሊ ፎር ዘ ካውንስል ኦፍ ዩሮፕ” አባል ነኝ፡፡ 47 አገሮች በአባልነት ይገኙበታል፡፡ በስደተኞች ጉዳይና በተፈናቀሉ ሰዎች ዙሪያ እንወያያለን፡፡ አክራሪዎቹ እየጠነከሩ ነው፡፡ በግሌ ከባህልና ከሀይማኖት ጋር የተያያዙ  ግጭቶች መቀነስ አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ “ሮም ስትኖር ሮምን ምሰል” ይላል ተረቱ፡፡  የራስ ባህል ይረሳ ማለት አይደለም፡፡ እኔ የዛምቢያን ባህሌን ሳልረሳ የፖላንድን ባህል  ተምሬያለሁ፡፡ ፖላንድ ውስጥ በተካሄደ ጥናት፤ አክራሪዎች ከ7 በመቶ በታች ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር ሚዛን ሲኖረው ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡
በምስራቅ አውሮፓ በዘረኝነት ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠሩ አገሮች ውስጥ ፖላንድ አንዷ ናት፡፡ እንዲያውም ፖላንዳውያን ጥቁሮችን “ሙዢን” ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ እርስዎ ደግሞ በፖላንድ ፓርላማ ውስጥ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ እስቲ ስለዘረኝነቱ ጉዳይ ይንገሩኝ?
ሙዚን ማለት ኒገር ማለት ነው፡፡ ቃሉ እንደ አጠቃቀሙ ሁኔታ ነው ትርጉም የሚሰጠው። የሚቀርብሽ ሰው ሙዢን ሲልና እንደ ስድብ የሚጠቀምበት ሰው ሲያጋጥም ትርጉሙ ይለያያል። ሙዚን ማለት ቆዳው የጠቆረ ማለት ነው፡፡ ፖላንዳውያን እርስ በርስ ሲጠቀሙበት ችግር የለውም፤ ጥቁር የሆኑ ሰዎች ሙዢን ሲባሉ ግን የሚያስቀይም  ይሆናል፡፡  ይህ ቃል ጥቅም ላይ እንዳይውል የምንፈልገው አሉታዊ ነገር ስላለው ነው፡፡ እኛ ከሙዚኖች በአንድ መቶ አመት ያህል እንደምንርቅ ይነገራል፡፡ ይህ አባባል ሌሎችን ስለሚያስቀይም ጥቅም ላይ ባይውል እንመርጣለን፡፡ እኔ ተማሪ ሆኜ በመጣሁበት ጊዜ ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደማንኛውም ወጣት ተበሳጭቼና ግብግብ ገጥሜ አውቃለሁ፡፡ ያ ማለት ግን ፖላንዳውያን ዘረኞች ናቸው ማለት አይደለም። በመጀመሪያ ምርጫ ተወዳድሬ  እንዳሸነፍኩ ከዋርሶ ድረስ  እኔን ኢንተርቪው ለማድረግ የመጣ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ ሰዎችን ቃለመጠይቅ ሲያደርግ፤ “ምን ያስገርምሀል? ከዋርሶ ድረስ መጥተህስ ለምን ቃለ መጠይቅ ልታደርግልን ፈለግህ? እሱ ከኛ ጋር የኖረ የኛ ሰው ነው፤ ስለዚህ  መረጥነው” በማለት መልሰውለታል። “እኛ የመረጥነው ኬለንን እንጂ ነጭ ወይም ጥቁር ብለን አይደለም” ብለውታል፡፡ አንቺ እንዳልሽው ስለ ፖላንድ ከዘረኝነት ጋር ተያይዘው ብዙ ነገሮች ይፃፋሉ፤ ነገር ግን የፖላንድ ፓርላማ እኔና አንድ ናይጄሪያዊን በፓርላማ አባልነት ይዟል።  ይህን ምን ትይዋለሽ?

  • የቲያትር ቤቱ አርቲስቶች 66 ስደተኞችን ከኬንያ ወህኒ ቤት አስፈቱ
  • ባለ 52 ክፍል ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ እያዘጋጁ ነው
  • ዝግጅቱ ሳይጀመር ከግማሽ ሚሊዬን ብር በላይ ፈጅቷል
  • በኬንያና ጅቡቲ በስደት ላይ የዳሰሳ ጥናት ተሠርቷል

        የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር፤በኬንያና ጅቡቲ ባለሙያዎችን በማሰማራት በህገወጥ ስደት ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት ያካሄደ ሲሆን ጥናቱን መነሻ በማድረግም ባለ 52 ክፍል ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ አዘጋጅቶ በአቢሲ ማስተላለፍ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡
የትያትር ቤቱ ባለሙያዎች አርቲስት ቴዎድሮስ በላይነህ፣ ደረጀ ደመቀ፣ ቴዎድሮስ ተስፋዬና እመቤት ወ/ገብርኤል በጅቡቲ ለ10 ቀናት፤ በኬንያ ለ8 ቀናት ቆይታ በማድረግ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዳቸውንና በጥናቱ መነሻነትም የቴሌቪዥን ድራማ እያዘጋጁ እንደሆነ ከትናንት በስቲያ በሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደ ውይይት ላይ አስታውቀዋል፡፡  
አርቲስቶቹ በሁለቱ አገራት በነበራቸው ቆይታ ስደተኞችን እስር ቤት ድረስ ሄዶ በማነጋገር፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ቃለ ምልልስ በማድረግና ስለ ስደተኞቹ የተሻለ መረጃ ያላቸውን ግለሰቦች በመጠየቅ መረጃዎችን እንዳሰባሰቡ የገለፁ ሲሆን ከጅቡቲ 320 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘው ኦቦኮ ወደብ በመጓዝም ጀልባ እየተጠባበቁ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ጭምር በማነጋገር ጥናቱን እንዳካሄዱ ተናግረዋል፡፡ በኬንያ የስደተኞች መንደርና በፖሊስ ጣቢያዎች እንዲሁም በፍ/ቤቶች በመገኘትም ስደተኞቹ የሚጋፈጡትን መከራ መታዘብ እንደቻሉ ጠቁመዋል፡፡ በጥናቱ ሂደት ላይም  በኬንያ የታሰሩ 66 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አጋጥመዋቸው፣ ናይሮቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመነጋገር ከእስር እንዳስፈቷቸው አርቲስቶቹ ተናግረዋል፡፡  
በሞያሌ አድርገው ኬንያ በመግባት፤ ታንዛኒያ፣ ማላዊና ዚምባብዌን አቋርጠው መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሙሉ በሙሉ ወንዶች መሆናቸውን የጠቆሙት አጥኚዎቹ፤ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከሁለት አካባቢዎች ብቻ (ከሃዲያና ከከንባታ ዞን) የሚጓዙ መሆናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን የቀሩት 5 በመቶ ደግሞ ከሻሸመኔ አካባቢ ደቡብ አፍሪካን አልመው በደላሎች እየታገዙ፣ ከስቃይና እንግልት ጋር በመጋፈጥ ከአገር እንደሚወጡ ለማወቅ ችለዋል፡፡   
የስደተኞቹ የእድሜ ክልል ከ14 እስከ 46 አመት ሲሆን ከ15 እስከ 28 አመት እድሜ ያሉት አብላጫውን ቁጥር እንደሚይዙ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ደቡብ አፍሪካን አልመው ከአገራቸው የሚወጡት እነዚህ ስደተኞች፤ እያንዳንዳቸው ከ60-80ሺ ብር ለደላሎች እየከፈሉ እንደሚጓዙ ጠቅሰው ከእስር ያስፈቷቸው 66 ስደተኞች በድምሩ 4.8 ሚሊዮን ብር ገደማ ለደላሎች እንደከፈሉ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡  
ስደተኞቹ የኬንያን ድንበር ሲያቋርጡ በፀጥታ ሃይሎች ከተያዙ፣“የሃገር ድንበር በመድፈር” ወንጀል ተከሰው ፍ/ቤት እንደሚቆሙ የጠቆሙት አጥኚዎቹ፤ በአብዛኛው የ1 አመት እስር፣ የ100ሺህ ሺሊንግ ቅጣትና ከፍተኛ የጉልበት ስራ እንደሚበየንባቸው ገልጸዋል - 66 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከዚህ ዓይነቱ ቅጣት ማዳናቸውን በማስታወስ፡፡
ስደተኞቹ በፀጥታ ሃይሎች ሲያዙና ፍ/ቤት ሲቀርቡ የተለያዩ የፈጠራ ሰበቦችን ይሰጣሉ ያሉት አጥኚዎቹ፤ ፍርድ ቤት ከመግባታቸው በፊት ደላሎችና አስተርጓሚዎች የሚሉትን እንደሚያስጠኗቸው ጠቁመዋል፡፡  እዚያ በነበሩበት ወቅትም “ኢትዮጵያና ኤርትራ ሊዋጉ ስለሆነ ከብላቴ ማሠልጠኛ አምልጠን ነው የመጣነው” ብለው እንዲናገሩ ሲመከሯቸው መታዘባቸውን አርቲስቶቹ ገልጸዋል፡፡  
አንዳንዶቹ ስደተኞቹ ደቡብ አፍሪካን ብቻ አልመው ከአገር እንደሚወጡና ከዚያ ውጭ ምንም ግንዛቤ እንደሌላቸው ያስረዱት አጥኚዎቹ፤ በአንድ ወቅት ኬንያ የገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከተባበሩት መንግስታት የጥገኝነት ፍቃድ አግኝተው ወደ አውስትራሊያ እንዲሄዱ ቢነገራቸውም ከደቡብ አፍሪካ ውጭ የትም አንሄድም ብለው አሻፈረን ማለታቸውን በማስረጃነት ጠቅሰዋል፡፡
ለኢትዮጵያውያን የህገወጥ ስደት ህገወጥ ደላሎች ሚናቸው የጎላ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚነገር ሲሆን ኬንያ ውስጥ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የኬንያ ደላሎች እንደሚበዙ አርቲስቶቹ ጠቁመው ዋነኛዋ ደላላ  የሃድያ ተወላጅ ኢትዮጵያዊት መሆኗን ደርሰንበታል ብለዋል፡፡ ደላላዋ ስሟን አንዴ አስካለ፣ ሌላ ጊዜ የሺ…እያለች እንደምትቀያይርም ገልፀዋል፡፡
ወደ ኬንያ የሚደረገው ጉዞ በእግርና በመኪና ሲሆን በሞያሌ በኩል በመኪና የሚገቡት ስደተኞች፤ ከፍየልና ከበግ ጋር ተጭነው እየሸኑባቸው እስከ 700 ኪ.ሜ ርቀት ይጓዛሉ ተብሏል፡፡ ከሞያሌ በኋላ ናይሮቢ ለመድረስ ስደተኞቹ በሁለት አቅጣጫዎች  እንዲጓዙ ይደረጋሉ፡፡ እነኚህ አቅጣጫዎችም “ቦስኒያ” እና “ፋክስ” በመባል ይታወቃሉ፡፡ “ፋክስ” አቆራራጭ መንገድ በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ሲሆን “ቦስኒያ” ስቃይ የበዛበት መንገድ መሆኑን ለመጠቆም የተሰጠ ስያሜ ነው ብለዋል፤ አጥኚዎቹ፡፡ ከናይሮቢ 400 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አስዬሎ፤ ሁለተኛዋ የስደተኞች ማከፋፈያ ከተማ ስትሆን ደላሎች እንደ ችርቻሮ እቃ ስደተኞቹን ተከፋፍለው በየአቅጣጫው የሚያሠማሩባት ከተማ እንደሆነች አጥኚዎቹ ይናገራሉ፡፡  አርቲስቶቹ በጅቡቲ ባደረጉት ጥናትም፣ስደተኞች በዚህ ድንበር አቋርጠው ሳኡዲ ለመግባት የከፋ ስቃይ እንደሚጋፈጡ ለማወቅ ችለዋል፡፡ የጅቡቲውን አስከፊ የሚያደርገው ስደተኞች በከፍተኛ ሀሩርና በረሃ ከ10-12 ቀናት በደላሎች እየተመሩ፣ በእግር መጓዛቸው ሲሆን እያንዳንዱ ስደተኛም ለደላሎች እስከ 10ሺህ ብር የሚደርስ ክፍያ መፈፀም ይጠበቅበታል፡፡
አጥኚዎቹ እንደገለጹት፤ስደተኞቹ በብዛት ከሀረር፣ ድሬደዋ፣ ወሎና ትግራይ የሚሄዱ ሲሆን ከአንድ አመት ተኩል ወዲህ ደግሞ ከጅማ አካባቢ ወደ ጅቡቲ የሚያቀኑ ስደተኞችም ተበራክተዋል፡፡ ከወሎና ትግራይ አካባቢ የሚሄዱት ስደተኞች የተሻለ ገንዘብ ያላቸው በመሆኑ የሚጠየቁትን በቅድሚያ ከፍለው እንደሚጓዙ የተናገሩት አርቲስቶቹ፤ በተለይ ከጅማ አካባቢ የሚመጡት ግን በገንዘብ እጦት ቶሎ ወደ የመን ባለመሻገራቸው እዚያው መስጊድ ሠርተው  በተስፋ እስከመኖር መድረሣቸውን እንደታዘቡም ጠቁመዋል፡፡ በኦቦክ ወደብ ለሁለትና ሶስት ወራት ያህል በረሃብና በእርዛት የሚቀመጡት በአብዛኛው  የጅማ፣ የሃረርና ድሬደዋ ስደተኞች ናቸው ይላሉ - አርቲስቶቹ፡፡
በጅቡቲ መስመር ከሚወጡት ስደተኞች መካከል አብላጫውን ቁጥር የያዙት ወንዶች ሲሆኑ የሴቶቹም ድርሻ ቀላል አይደለም ተብሏል፡፡ ሴቶቹ ብዙ ጊዜ ተደብቀው እንደሚቆዩና ሌሊት 10፡30 አካባቢ ባህሩ ዳርቻ ላይ ተሰባስበው እንደሚታዩ ተገልጿል፡፡ አጥኚዎቹ፤ በጅቡቲ ኦቦኮ ወደብ በደረሱበት ወቅት 10ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች ተኮልኩለው ጀልባ ሲጠባበቁ መመልከታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የስደቱ መነሻ በዋናነት የኢኮኖሚ ጥያቄ አለመሆኑን በተለይ ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚጓዙ ስደተኞችን በመጥቀስ የተናገሩት አርቲስቶቹ፤ ለስደቱ መነሻ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የቤተሰብ ወይም ወዳጅ ዘመድ ግፊትና የአመለካከት ችግር እንደሆነ ተገንዝበናል ብለዋል፡፡ “ስደተኞቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ የሚያወጡት ወጪ ሲሰላ፣ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ ኬንያዊ ካለው አመታዊ ገቢ ጋር የሚተካከል ነው” ያሉት አጥኚዎቹ፤ አብዛኞቹ ቤት፣ ተሸከርካሪና ሌሎች ንብረቶች ያላቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
አርቲስቶቹ እዚህ ማጠቃለያ ላይ ለመድረስ የሚያበቃ የተሟላ ጥናት አላደረጉም ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፤ ከጅቡቲና ኬንያ ውጭ በአገር ቤት የስደተኞቹ መነሻ መንደሮች በጥናቱ ውስጥ አመለካተታቸው በራሱ የማጠቃለያውን ትክክል አለመሆን ያሳያል ብለዋል፡፡ “ለደላሎች ይከፈላል የተባለው ከፍተኛ ገንዘብ ምንጩ ምንድነው? የቤተሰብ ሃብት፣ ብድር ወይስ ራሳቸው ያፈሩት ጥሪት?” በማለት የጠየቁት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ የአርቲስቶቹ ጥናት ይሄን በአግባቡ ሳይመልስ ለድምዳሜ የተጣደፈ ይመስላል ሲሉ ተችተዋል፡፡
በውይይቱ ከተካፈሉ ታዳሚዎች በተሰነዘረው አስተያየትም፤ አርቲስቶቹ ጥናቱን መሠረት አድርገው ድራማውን ሲፅፉና ሲያዘጋጁ አሣማኝ የሆኑ ለስደት የሚዳርጉ ምክንያቶችን ማቅረብ እንዳለባቸው ጠቁመው ለዚህም የስደተኞች መነሻ መንደሮች ድረስ በመዝለቅ ጠለቅ ያለ ጥናት ማድረግ ይበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ሌሎች በሣይንሳዊ መንገድ በሚገባ የተጠኑ ጥናቶችንም ማጣቀስ እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡
በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ተመስርቶ በ52 ክፍሎች የሚዘጋጀው ድራማ፤ በኢቢሲ ለተመልካች እንደሚቀርብ የተገለፀ ሲሆን እስካሁን ለፕሮጀክቱ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንና አብላጫውን ወጪ የሸፈነውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሆነ ታውቋል፡፡ የስደቱን ድራማ የሚፅፈው አርቲስት ደረጀ ደመቀ ሲሆን በማዘጋጀቱ በኩል ቀሪዎቹ የቡድኑ አባላት ይሣተፉበታል ተብሏል፡፡ በሱዳን መስመር ያለውን ህገወጥ የስደት እንቅስቃሴም ትያትር ቤቱ እንደሚያስጠናና የድራማው አካል እንደሚያደርገው አርቲስቶቹ ጠቁመዋል፡፡ አርቲስት ደረጀ እስካሁን የድራማውን 35 ክፍሎች ስክሪፕት እንደፃፈና በቀሪው 17 ክፍል የሱዳኑን የጥናት ውጤት አካትቶ እንደሚፅፍ ተናግሯል፡፡ የቴሌቪዥን ድራማው መቼ ለዕይታ እንደሚበቃ ግን አልተገለጸም፡፡ “በቀጣይ የሚታወቅ ይሆናል” ተብሏል፡፡  

    ወቅቱ 1973 ዓ.ም ነበር፡፡ አገሪቱ ከተለያዩ የውስጥና የውጪ ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ የገባችበት ጊዜ ነው፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ልጆቻቸውን ያለ አሳዳጊ ጥለው በየጦር ሜዳው ወድቀዋል፡፡ አሳዳጊና ተንከባካቢ ያጡት ህፃናት በየጎዳናው መውደቃቸው ያሳሰበው የደርግ መንግስት፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በነበሩት መንግስቱ ኃይለማርያም ልዩ ትዕዛዝ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ህፃናት አምባ ተቋቁሞ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
በቀድሞ አጠራር በሸዋ ክፍለ ሃገር ሀይቆችና ቡታጅራ አውራጃ፣ በአላባ ቁሊቶ ወረዳ፣ አላጌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወላጆቻቸውን በጦርነትና በሌሎችም ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ያጡ ህፃናትን ተቀብሎ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን በማሟላት፣ በትምህርትና በሥነ ምግባር ኮትኩቶ የማሳደግን ዓላማ አንግቦ የተቋቋመው አምባው፤ “ሰብለ አብዮት”፣ “መስከረም ሁለት ኦጋዴን”፣ “ዘርዓይ ደረስ” እና “መንግስቱ ኃ/ማርያም” በተባሉ 5 መንደሮች የተከፋፈለ ነበር፡፡
አምባው ገና ከተወለዱ ህፃናት ጀምሮ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ህፃናትን ተቀብሎ እያሳደገ ያስተምርና ዕድሜያቸው 18 ዓመት ሲሞላ (የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ) ከማሳደጊያው ይሰናበታሉ፡፡ ህፃናቱ አምባውን ለቀው በሚወጡ ጊዜ በስነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑና በማህበራዊ ህይወታቸውም የመገለል ስሜት እንዳያድርባቸው ልዩ የምክር አገልግሎት ይሰጣቸው እንደነበር የቀድሞው የአምባው ልጆች ያስታውሳሉ፡፡ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያገኙ ተማሪዎች አንድም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገባሉ አሊያም ወደ ውጪ አገር (በአብዛኛው ኩባና ራሺያ) እየሄዱ ይማሩ ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም የአምባው መስራችና ህፃናቱ ሁሉ ”አባታችን“ እያሉ የሚጠሯቸው የአገሪቱ መሪ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም አገር ጥለው መውጣት ለአምባው ህፃናትና ሰራተኞች ትልቅ ዱብ እዳ ነበር፡፡
የአምባው ህፃናት መሳጭና መልእክት አዘል በሆኑት ህብረ ዝማሬዎቻቸው በእጅጉ ይታወቁ ነበር፡፡ በታዋቂዋ ገጣሚ አለምፀሐይ ወዳጆ ክትትልና የጥበብ ስልጠና ይደረግላቸው የነበሩት የአምባው ልጆች፤ “የጀግና ፍሬ” በተሰኘ የኪነት ቡድን ታቅፈው በየጊዜው ለታዳሚዎች የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችን ያቀርቡ ነበር፡፡ በዚህ ቡድን ተዘጋጅተው ለአድማጭ ጆሮ ከበቁትና ተወዳጅነትን ካገኙት ስራዎቻቸው መካከል “ፀሐዬ”፣ “የጀግና ልጅ ጀግና” እና “እርግቢቱ ሂጂ” የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በ1970ዎቹ መገባደጂያና በሰማንያዎቹ መጀመሪያ ላይ አብዛኛው ታዳጊ እኒህን መዝሙሮች ከህዝብ መዝሙር ባልተናነሰ ያውቃቸው ነበር፡፡ በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም መዝሙሮቹን በተደጋጋሚ መስማት አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ የደርግን ውድቀት ተከትሎ ግን መዝሙሮቹ ታሪክ ሆነው ተረሱ፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላም በቅርቡ እኒህ ሥራዎች በከፊል የተካተቱበት ሲዲ ታትሞ መውጣቱ ተሰምቷል፡፡
እኔም አጋጣሚውን በመጠቀም የሙዚቃ ሥራው አስተባባሪ የሆኑትንና የአምባው ልጆች የነበሩትን መቅደስ ተመስገን እና ጆኒ መርጊያ ስለ ህፃናት አምባው፣ ስለ አስተዳደጋቸው፣ በተለይ ከፕሬዚዳንት መንግስቱ ጋር ስለነበራቸው ቁርኝትና ከአገር መውጣታቸውን ሲሰሙ ስለተፈጠረባቸው ስሜት እንዲሁም ስለ መዝሙሮቻቸው እንዲያወጉኝ ጠየቅኋቸው፡፡ በደስታ ፈቃደኝነታቸውን ገለፁልኝ።
የአምባ ህይወት ጅማሮ (ጆኒ መርጊያ)
“በወላጅ አባቴ የአዕምሮ ህመም ምክንያት ቤተሰባችን ሲበተን እኔ ገና ህፃን ልጅ ነበርኩ። እናታችን ሁኔታውን መቋቋም ተስኗት ጥላን ጠፋች፤ ስለዚህም አንድ ወንድሜና እህቴን ጨምሮ ሶስታችንም ጎዳና ወጣን፡፡ ወቅቱ ለእኛ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ የሚላስ የሚቀመስ አጥተን በረሃብ ከመሞታችን በፊት ግን ከጎዳና ላይ ተለቅመን እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ የህፃናት ማሳደጊያ ተቋም ውስጥ እንድንገባ ተደረግን፡፡ በ1973 ዓ.ም መንግስት አባቶቻቸውን በጦርነት ያጡትን ህፃናት ሰብስቦ ለማሳደግና ለማስተማር በማሰብ የኢትዮጵያ ህፃናት አምባ እንዲቋቋም አደረገ፡፡ የህፃናት አምባው ግንባታ ተጠናቆ በዚያው ዓመት አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም ከየጎዳናው እየተለቀሙ በህፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ እንዲቆዩ የተደረጉት ህፃናት እየተሰበሰቡ ወደ አምባው እንዲገቡ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡ በዚህ መሰረትም እኔና አንድ ወንድሜ ወደ ህፃናት አምባው ገባን፡፡”
መቅደስ ተመስገን (10 ዓመታትን በአምባው ያሳለፈች)
“ወደ አምባው የገባሁት የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር፡፡ አባቴ ወታደር ስለነበር አስመራ ውስጥ በግዳጅ ላይ ህይወቱ በማለፉ፣ከልጆቹ መካከል ህፃናት አምባ የሚገባ ልጅ ሲጠየቅ፣ እኔ ከቤተሰቦቼ ተለይቼ ወደ አምባው እንድገባ ተደረገ። ወደ አምባው ስገባ የነበረውን ሁኔታ ፈፅሞ አልረሳውም፡፡ በአንዲት ጠባብ ቤት ውስጥ ከጥቂት የቤተሰብ አባላት ጋር በአንድ ትሪ ትበላ ለነበረች ህፃን፣ በትልቅ የምግብ አዳራሽ እጅግ በተዋበ ገበታ ላይ ከብዙ ህፃናት ጋር እንድትበላ ስትደረግ የሚፈጠርባትን ስሜት ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ማታ ቴሌቪዥን ልናይ ወደ አዳራሽ ስንገባ፣ በእውኔ ሳይሆን በህልሜ ነበር የመሰለኝ፡”
የአምባው ትዝታ
“አምባው፤አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ማግኘት ያለበትን ደስታና ፍቅር አግኝተን ያለፍንበትና ለህይወታችን መሰረት የሆነን ዕውቀት የቀሰምንበት ቦታ ነው፡፡ ራሳችንን በአግባቡ መግለፅ የምንችል፣ በራሳችን የምንተማመን ልጆች ሆነን እንድናድግ ያደረገን አምባው ነው፡፡ የምግብ፣ መጠጥና አልባሳት  ጭንቀት ሳይኖርብን፣ የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ተሟልቶልን ነው ያደግነው፡፡ ከዚሁ ሁሉ በላይ ደግሞ አሳዳጊዎቻችን ተገቢውን የቤተሰብ ፍቅርና እንክብካቤ እየሰጡ አሳድገውናል፡፡ ይህ ቀረብን የምንለው ነገር ፈፅሞ የለም፡፡
“ክረምት ሲመጣ ቤተሰብ ያላቸው ልጆች ወደ ቤተሰቦቻቸው ጋ በመሄድ፣ ሁለቱን ወራት የእረፍት ጊዜ እዚያ አሳልፈው ይመጡ ነበር፡፡ ይህ የሚደረገውም ከቤተሰቦቻችንም ሆነ ከማህበረሰቡ የራቀ ህይወት እንዳይኖረንና ውጪውን እንድንላመድ ነው፡፡ ቤተሰብ የሌላቸው ልጆችም ክረምቱን በጓደኞቻቸው ቤተሰቦች ቤት እየሄዱ ያሳልፉ ነበር። ህፃናቱ የእረፍት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ አምባው ሲመለሱ፣ ከአምባው 32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቡልቡላ ከተማ ጊዜያዊ ፅ/ቤት ተቋቁሞ፣ የህፃናቱ የጤና ሁኔታ በባለሙያዎች እየተመረመረ ወደ አምባው እንዲገቡ ይደረግ ነበር።”
የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም፤ ህፃናቱ አስፈላጊው ነገር ሁሉ እየተሟላላቸው እንደሆነ ለማየት የቅርብ ክትትልና ድንገተኛ ጉብኝትም ያደርጉ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የአምባው ህፃናት ከምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ቅሬታ አንስተው “አባታችን ይጠራልን” በማለታቸው ፕሬዚዳንቱ ወደ አምባው ሄደው ልጆቹን አነጋግረው ተመልሰዋል፡፡ ይህንን ሁኔታ እነ መቅደስ እንዲህ ያስታውሱታል፡-
“ፕሬዚዳንት መንግስቱ ለእኛ የተለየ ፍቅር ነበረው፡፡ እኛም እንደዚሁ እኛን ለመጐብኘት ወደ አምባው ሲመጣ በውስጣችን ይፈጠር የነበረውን ልዩ ስሜት ለመግለፅ ያዳግተናል፡፡ በየጊዜው እየመጣ ያዋራንና ያበረታታን ነበር፡፡ አሳዳጊዎቻችን እንኳን “እንዲህ አደረጉ… ጠገቡ” ብለው ሲነግሩት፤ “ተዉ ልጆቻችሁ ቢሆኑ እንዲህ አትሉም ነበር” ይላቸዋል፡፡ አንድ ጊዜ በአምባው ውስጥ ከምግብ ጋር የተያያዘ ቅሬታ ተነሳና ረብሻ ተፈጠረ፡፡ ከእኛ በላይ ያሉ ተማሪዎች “አባታችን ይጠራና ያነጋግረን” ብለው ጠየቁ፡፡ በእሱ ምትክ ፍስሃ ደስታ ወደ አምባው መጡ፡፡ ማንም ግን ሊያነጋግራቸው አልፈለገም፡፡ “ራሱ አባታችን ይምጣ” ብለው ድርቅ አሉ፤ ተማሪዎቹ፡፡ በኋላም መንግስቱ መጣና ሊያነጋግረን ሰበሰበን፡፡ ከተለያዩ ኃይሎች ጋር ከባድ ጦርነት ላይ እንደሆነና በየቀኑ ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ለመሳሪያ ግዥ እንደሚያወጣ ነገረን፡፡ እናም ታገሱን፣ ተረዱን አለን፡፡ እኛንም አሳዳጊዎቻችንንም ለየብቻ አነጋግሮና አስማምቶን ሄደ፡፡ በየጊዜው ወደ አምባችን እየመጣ ያፅናናንና ያነጋግረን ነበር፤ በኋላ በኋላ ግን መምጣቱን ተወው፡፡”
ፕሬዚዳንቱ ከአገር ሲወጡ …
ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም ከአገር የመውጣታቸው ዜና ለአምባው ህፃናትና ሰራተኞች ለመሸከም የሚያዳግት ክፉ መርዶ ነበር፡፡ ህፃናቱም ሆኑ አሳዳጊዎቻቸው ቀጣይ እጣ ፋንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ባለማወቃቸው በእጅጉ ተደናገጡ። በተለይ የአምባው ሰራተኞችና አሳዳጊዎቻቸው የተቋሙ ሰላምና የህጻናቱ ህይወት ያሳስባቸው ነበር። አምባው የተሰራበት ቦታ የአሩሲና አላባ ተወላጅ የሆኑ ወገኖችን የሚያወዛግብ ስለነበር በተፈጠረው ክፍተት አንዱ ወገን በህፃናቱ ላይ አደጋ እንዳይጥል ስጋት ነበረባቸው፡፡
“እናም ችግሩ በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበትን መንገድ ለመፈለግ  የአምባው ስራ አስኪያጅ በአገር ሽማግሌ ልመና ይዞ ነበር፡፡ እኛም በማንኛውም ጊዜ ለሚደርሰን ትዕዛዝ ዝግጁ ሆነን በተጠንቀቅ እንድንጠባበቅ ስለተነገረን፣ ራሳችንን ለጉዞ አዘጋጅነት ነበር፡፡ በኋላ ግን የኢህአዴግ ወታደሮች ወደ አምባው በመምጣታቸው ሊፈጠር የነበረው ችግር ተወግዶ ሰላማዊ ህይወታችንን ለመቀጠል ችለናል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከአገር ወጥተዋል የሚለው ዜና በሬዲዮ ሲሰማ፣ ሁላችንም ሰማይ ምድሩ ነበር የዞረብን፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላስ?
ከደርግ ውድቀት በኋላ በአምባው ለሚኖሩ ህፃናትና ታዳጊዎች የሚደረገው እንክብካቤ በእጅጉ ቀንሶ ነበር፡፡ ልጆቹ እንደቀድሞው ዓይነት እንክብካቤ እንደማይደረግላቸውና አርፈው ትምህርታቸውን መማር እንደሚገባቸው በግልፅ ተነገራቸው፡፡
“መንግስት እንደተቀየረ ይደረግልን የነበረው እንክብካቤ ተቀየረ፡፡ አዳራሽ ሰብስበውን እንደ ድሮው እንደልብ ሆኖ መኖር የለም፡፡ አርፋችሁ ተማሩ አሉን፡፡ ይህ  ለእኛ ምን አይነት ስሜት እንደሚፈጥርብን መገመት አያስቸግርም፤ ሁኔታው በትምህርት ውጤታችን ላይም ተፅዕኖ አሳድሯል። አምባው ደርግ የወታደሮቹን ልጆች ለማሳደግ የከፈተው ነው በሚል እንዲፈርስ  ተደረገ፡፡
አምባው እንዴት ፈረሰ?
የኢትዮጵያ ህፃናት አምባ በአዋጅ እንዲፈርስ የተደረገው በ1989 ዓ.ም ነበር፡፡ ልጆቹ የክረምቱን የእረፍት ጊዜ ከቤተሰቦቻቸውና ከየጓደኞቻቸው ጋር ለማሳለፍ አምባውን ለቀው የወጡበት ወቅት ነው፡፡ ምንም ቤተሰብና ጠያቂ የሌላቸው በርካታ ልጆችም በአምባው ውስጥ ክረምቱን እያሳለፉ ነበር፡፡ አምባው እንደሚዘጋና ልጆቹ እዚያ ባሉበት ቦታ ሆነው ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚያሳስብ መልእክት በሬዲዮ ተላለፈ፡፡ ይህ መልእክት የበርካታ የአምባው ልጆችንና ሕፃናትን የወደፊት ህይወት ያጨለመ እንደነበር ልጆቹ ይናገራሉ፡፡
“የአምባ ልጆች ማለት የውጪውን ዓለም እምብዛም የማያውቁ፣ ጠያቂ ዘመድና ቤተሰብ ያልነበራቸው ናቸው፡፡ ይህንን መርዶ ለእነዚህ ልጆች መንገር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የደረሰበት ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ የራሳቸው ቤተሰብ የሌላቸው፣ ክረምቱን ጓደኞቻቸው ቤተሰቦች ቤት ለማሳለፍ የሄዱ ህፃናት አያሌ ነበሩ፡፡ እነዚህ ህፃናት መግቢያቸው የት ነው? ከሁሉ የሚያሳዝነው ደግሞ በአምባው ውስጥ ክረምቱን ለማሳለፍ በቆዩት ልጆች ላይ የተፈፀመው ነገር ነው፡፡ ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ የሆኑትን ልጆች ሰብስበው ዝዋይ ከተማ ወስደው ሜዳ ላይ በተኗቸው፡፡ በዚህም የተነሳ አብዛኞቹ ለሞት፣ ለስደትና ለቡና ቤት ህይወት ተዳርገዋል፡፡ ዕድሜያቸው አነስተኛ የሆኑትን አዲስ አበባ ቀጨኔና ሚኪሊላንድ ህፃናት ማሳደጊያ አስገቧቸው፡፡ በዚህ መንገድ ከአምባው የወጡት ልጆች ወደ ማህበረሰቡ ውስጥ ገብተው፣ በሰላም ተቀላቅለው ለመኖር ትልቅ ፈተናና ትግል ገጥሟቸው ነበር፡፡ ምንም ዓይነት የስነልቦና ዝግጅት ስላልነበረን ሁኔታውን መቋቋም ተስኖን ነበር። አምባው ስራውን ያቋረጠው ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ በድንገት ነበር፡፡”
የአምባው ፍሬዎችና አይረሴ
መዝሙሮቻቸው
የአምባው ህፃናት ከ50 በላይ ህብረ መዝሙሮች የነበሯቸው ሲሆን ከእነዚያም ውስጥ ጥቂቶቹን አሰባስበው በቅርቡ በሲዲ በማስቀረጽ ለገበያ አቅርበውታል፡፡ “የህፃናት አምባ ልጅ ሆኖ መዝሙር የማይችል የለም፡፡ ታዋቂ ደራሲያንና የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ወደ አምባ እየመጡ ያሰለጥኑን ነበር፡፡  የአምባ የጀግና ፍሬ በሚባለው የኪነት ቡድን ታቅፈን የሰራናቸው ከ50 በላይ ህብረ መዝሙሮች አሉን፡፡ አሁን አምባው ከፈረሰና ከተበተንን ከዓመታት በኋላ ባቋቋምነው “የአምባ አብሮ አደግ መረዳጃ እድራችን” ሙሉ ወጪው ተሸፍኖ መዝሙሮቻችን በሲዲ ታትመው ወጥተዋል፡፡ ሲዲውን ለመስራት ያነሳሳን  የአምባ ልጆችን ሊያግባባና አንድ ሊያደርገን የሚችል በእጃችን ላይ የቀረ የድሮ ነገር መዝሙሮቻችን ብቻ መሆናቸው ነው፡፡
በዚህ ዘመን ደግሞ መሀል ላይ ላለው ትውልድ ማለትም ለታዳጊው የሚሆን መዝሙር የለም፤ ስለዚህ ለምን መዝሙሮቹን አውጥተን አናሳትምም ብለን ተነጋገርንና ውሳኔ ላይ ደረስን፤ መዝሙሮቹን በልጆቻችን ልናዘምረው ነበር ያቀድነው ግን ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለዚህም ከአራት ኪሎ ህፃናትና ወጣቶች ትያትር ሁለት ህፃናትን ወሰድንና  ሰራነው፡፡” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
“በሲዲ የወጣው ስራችን አሳዳጊዎቻችን ለነበሩ ሰዎችና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋናችንን የምናቀርብበት እንዲሆን አድርገናል፡፡ አሁን እኛ ወላጆች ሆነን ስናየው፣ ልጆች ማሳደግ ምን ያህል ከባድና ፈታኝ እንደሆነ ተረድተናል፡፡ ስለዚህም አሳዳጊዎቻችን ሊመሰገኑና ሊከበሩ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡” ብለዋል የቀድሞ የአምባው ልጆች፡፡
የአምባው ልጆች ቅሬታ
“ህፃናት አምባው በጦርነትና በተፈጥሮአዊ አደጋዎች ወላጆቻቸውን ያጡ፣ አሳዳጊና ተንከባካቢ  የሌላቸው ልጆች እንዲያድጉበት ታስቦ የተሰራና ህፃናት በስነ ምግባርና በትምህርት የሚታነጹበት ስፍራ ነበር፡፡ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ይዘት አልነበረውም፡፡ አምባው በዚያ መንገድ መፍረሱ የሚያሳዝን ቢሆንም ከዚያ የበለጠ አሳዛኙ ጉዳይ ግን የአምባው ታሪክና ስራ ሁሉ እንዲጠፋ መደረጉ ነው፡፡
ታሪካችን ብጥስጥስ ብሎ ወድቋል፤ ጠፍቷል። እኛ ስንወጣ ልጆች በመሆናችን ይዘነው የወጣነው ምንም ነገር የለም፤ ግን የአገር ታሪክ ነው፤ ትውልድ ቢማርበት ጥሩ ነበር፡፡ ይህ አልሆነም፤ ታሪካችን በታሪክነቱ እንዲቀመጥ ባለመደረጉ እናዝናለን፡፡” ሲሉ ልጆቹ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡          

Published in ህብረተሰብ

የሃሜት ‹ብሬኪንግ ኒውስ› ከመሆን ያድነንማ!

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የሆነ መዝናኛ ቦታ ነው፡፡ (እኔ የምለው…ከተማዋ ሁሉ በሬስቱራንትና በምሽት ክበብ ተሞላች ማለት ነው! ልክ ነዋ…ከዛሬ፣ ነገ “የኮምፒዩተር ቺፕ ፋብሪካ…” ይከፈታል፣ “የኑክሌር ማብላያ…” ምናምን ነገር ይመረቃል እያልን ስንጠብቅ የሚከፈተው ምግብ ቤት፣ ‘ሲፕ’ ቤት፣ ‘ኩሼ’ የሚባልበት ቤት…ምናምን ነገር ሆኗል፡፡ እንግዲህ…ዋና ችግሮቻችን እነሱ ከሆኑ ይሁና! በቀደም በቲቪ ያየነው ሬስቱራንት የሚወስድ አቅም ያለው ወዳጅ እስኪደውልልን እየጠበቅን ነው፡፡)  
እናላችሁ…እዚህ መዝናኛ ቦታ ቁጭ ብለን አጠገባችን ‘የሰለጠኑ’ የሚመስሉ ሦስት ወንዶች ነበሩ፡፡ (የምር ግን…‘ስልጣኔ ምንድነው?’ በሚባለው ነገር ላይ አገር አቀፍ ኮንፍረንስ ምናምን ነገር ያስፈልገናል፡፡ (ለ‘ስንቱ ነገር’ እንሰበሰብ የለ እንዴ!) ልክ ነዋ…በፊት ‘የእርጥቦች ነገር’ የምንለው ነገር ሁሉ አሁን…‘የጨሱ’ ሰዎች የሚያደርጉት ሲሆን የሆነ ቦታ ላይ የተለወጠ ነገር አለ፡፡  እናላችሁ… ስለሆነ ጓደኛቸው ‘የመኝታ ቤት ታሪክ’ ነበር የሚያወሩት፡፡ ይሉት የነበረውን ነገር መጥቀስ…አሪፍ አይሆንም፡፡ ምን አለፋችሁ…የሆነ ‘የፖርኖ መጽሐፍ’ የሚተርኩ ነበር የሚመስሉት፡፡ የሆነ ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’ ምናምን በሉት፡፡
የሚገርመው ነገር ምን መሰላችሁ… ልክ የአዳራሹ ድምጽ ማጉያ አልሠራ ብሎ ሰብሳቢው ጮክ ብሎ እንደሚያወራው… አለ አይደል…እነሱም ድምጻቸውን ጥግ ድረስ ለቀው ነበር የሚያወሩት፡፡ ምን አለፋችሁ… መዝናኛው ውስጥ የነበረውን ሰው ከመጤፍ አልቆጠሩትም፡፡
እግረ መንገዴን..እንነዴ የሬስቱራንቱና ሻይ ቤቱ ይሄን ያህል እያስጮኸ የሚያስወራን…ምን ጉድ መጥቶ ነው! ስልጣኔ እኮ የሌላኛውን ሰው መብትም ማክበር ነው፡፡ ‘ባለማንበብዎ እናመሰግናለን’ አይነት ለታሪክ የሚቀመጥ ነገር ከመለጠፍ….‘እባካችሁ ስታወሩ ድምጻችሁን ዝግ አድርጉ…’ ምናምን የሚል ነገር ቢለጥፉ ይሻላል፡፡
ሌላ ደግሞ… ሁለት  አሳላፊዎች ለመቶ ሰው በተመደቡበት ቡና ምናምን መባያ ውስጥ… “ካምቦሎጆ ኳስ አለ እንዴ!...” የሚያሰኝ ጭብጨባ አሥር ጊዜ የምናጨበጭብ ሞልተናል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ… ጸጥ ያለ፣ አእምሮ ማሳረፊያ የሚባል አይነት መዝናኛ ማግኘቱ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሀሜት የሚሉት ነገር ምን ደረጃ እንደደረሰ የሚያሳይ አይመስላችሁም? ልክ ነዋ… በፊት አፍና ጆሮ እየገጠሙ በሹክሹክታ የሚነገረው ሁሉ በአደባባይ ሲወራ…ያውም የሰለጠኑ በሚመስሉ ሰዎች… የምር አስቸጋሪ ነው፡፡
እናላችሁ…‘በማያገባን እየገባን’ የሰውን ‘የአንሶላ ቀለም’ ካላወቅን የምንል ሰዎች ስንበዛ አሪፍ አይደለም፡፡ (እንትናዬ… ‘ቤድሺቱን’ ቡራቡሬ አደረግሽው የሚባለው እውነት ነው እንዴ! እንኳንም አደረግሽው፡፡ ልክ ነዋ…ከላይ እስከ ታች ነገረ ሥራችን ሁሉ ‘ቡራቡሬ’ በሆነበት ምን በወጣሽ አንድ ቀለም ብቻ!)
ስሙኝማ… ‘አማሪካኖቹ’…በተለይ የታዋቂ ሰዎችን የጓዳ ኑሮ ማውራት… አለ አይደል…የለመዱት ብቻ ሳይሆን…የ‘ቢዙ’ ጉዳይ ነው፡፡ (‘የሌሎችን መቅዳት’ ለመደብንና…እኛም አሁን፣ አሁን እንደዛ አይነት ነገር እየለመደብን ነው፡፡ ስሙኝማ…ታዋቂ ሰዎቻችን፣ መቼም ስንት ነገር ሹክ ሲባል እንሰማ መሰላችሁ! ነገ ተነገ ወዲያ ‘ኢ.ቲ’… ‘ዘ ኢንሳይደር’ ምናምን የተጀመረ ዕለት… አቤት ያኔ!…)
እናማ…የእኛ ችግር’ኮ፣ ምናምኒት፣ ‘ቤሳ ቤስቲኒ’ የሌለው ሰው የግል ህይወት ሁሉ… አለ አይደል…‘ብሬኪንግ ኒውስ’ ምናምን ነገር ሲሆን ቀሺም ነው። ቢለብሱም ባይለብሱም፣ ቢታዩም ቢደበቁም፣ ቢዘፍኑም ቢያለቅሱም፣ ቢወዱም ቢጠሉም…ምን አለፋችሁ…ምንም ነገር ቢሆኑ ‘ከሀሜት መትረፍ’ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ ‘ጨዋነት’ ምናምን የሚባለው ነገር ሁሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አይነት ነገር ሆኖ ቀረ ማለት ነው! የምር ግን…ከዚህ ቀደም እንዳወራነው ዓይናፋርነት …‘የጨዋነት’ መገለጫ መሆኑ ቀርቷል፡፡ እንደውም የአእምሮ ችግር አይነት ነገር ሊሆን ምንም አልቀረው።
እናላችሁ…‘ጨዋ አንገቷን የደፋች፣ ቀና ብላ ሰው የማታይ…’ ምናምን የሚለው መለኪያ ፊልም ላይ እንኳን እየቀረ ነው፡፡ (ከአእምሮ ጤንነት፣ ወይም ከስሜት መዛባት ከመሳሰሉ ነገሮች ጋር የሚመጣ፣ የባለሙያ ክትትል የሚይስፈልገው ዓይነአፋርነት’ የሚመስሉ ነገሮች እንዳሉ ሳንረሳ ማለት ነው፡፡)
እኔ የምለው… ነገርዬው ይብራራልና!” ልክ ነዋ…‘ዓይናፋር’ ስትገጥም የምንወስደው እርምጃ ግራ እንዳይገባን ነገሩን ‘አድምቶ የሚነግረን’ ያስፈልገናል። … “ጉዞ ወደ ሀኪም ቤት ነው ወይስ ‘የክፉ ቀን’ ኮንዶሚኒየም ወዳለው ጓደኛ!” ብሎ ለመወሰን ያስችላላ! እንትና… “ኮንዶሚየም ለኢመርጀንሲ እያገለገለ ነው…” ያልከኝ ለካስ እውነት ኖሯል!)
ኸረ መላ ምቱ ዘመድ ወዳጆቼ
ዓይናፋር ሆኛለሁ ዓይናፋር ወድጄ፣
የሚል ዘፈን ነበር…ያኔ ዓይናፋርነት ‘እሴት’ ምናምን ነገር በነበረበት ዘመን፡፡
እኔ የምለው…ትንሽ ወደ ቀልቡ የተመለሰ ይመስል የነበረው መብራት ደግሞ ጀመረው እንዴ! ምን ይደረግ… “አራት ቀን የጠፋው መብራት በአምስተኛው ቀን ሲመጣ ‘ኢሮ!’ ተብሎ የሚጨበጨብበት ዘመን ሊያልፍ ይሆን!” ብሎ ለመመኘት ጊዜ ሳይሰጠን ይሄን ሰሞን ሳናስበው…‘ድርግም’ ማለት ጀምሯል፡፡
ሀሳብ አለን…“ደግሞ፣ ደግሞ ጀመረኝ…” የሚለው ዘፈን ለኮረንቲዎችና እንደ ኮረንቲዎች ‘ደግሞ ለሚጀምራቸው’ እንዲሆን ግጥሙ ተቀይሮ “ኢሮ!” ከምንለው ጩኸታችንና ጭብጨባችን ጋር ‘ሪሚክስ’ ይደረግልንማ! ማስተካካያ… “ኢሮ!” ከሚለው ድምጽ ቀጥሎ በሹክሹክታ “ድንቄም!” የሚል ድምጽ በሹክሹከታ ይግባልን፡፡ ዘንድሮ ልጄ… ‘ዋና፣ ዋና’ ጉዳያችንን በሹክሹክታ ነዋ የምናወራው!)
በበፊት ጊዜ እናቶቻችንና እህቶቻችን በ‘ቡና ወሬ’ ምናምን በሚባለው ነገር ይታሙ ነበር፡፡ ዘንድሮ እሷ የለ፣ እሱ የለ…ሁላችንም ‘አንድ ሳጥን’ ውስጥ ሆነናል፡፡ የምር…ቡና ላይ ከሚወራው ሀሜት የማኪያቶውና ድራፍቱ ባይብስ ነው! ደግሞላችሁ… እንደሚነገረን ከሆነ ከዚሀ በፊት ነደልነው..የእንትናን ሚስት እኮ እንትን አልኳት እየተባለ የሚፎከርበት ዘመን ነው፡፡
‘የእንትናን ሚስት እንትን ማለት’ ለምስጢረኛ ጓደኛ የሚነግሩት ብቻ ሳይሆን በአደባባይ የሚፎክሩበት ሲሆን…ሀዲዱ የሆነ ቦታ ላይ አቅጣጫውን ስቷል ማለት ነው፡፡
እና እንትና… ‘ዋይፎቻችሁን’ ጠብቁ፣ ኋላ እኛ የለንበትም፡፡ የሚያሳስቱ ነገሮች በበዙበት ዘመን…“ምነው የማምንህ ወዳጄ አልነበርክም ወይ!” ብሎ…ዳኛ ፊት አቅርቡኝ አይነት አቤቱታ አይሠራም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የ‘ዋይፎችን’ ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን በሁለት ጓደኛሞች መካከል የተደረገች ልውውጥ ስሙኝማ…
“ለሚስቴ ቃል ልገባላት እፈልጋለሁ፡፡”
“ምን አይነት ቃል?”
“በሆነ ጊዜ ውስጥ ለልደቷ አርባ ሺህ ብር ልሰጣት ቃል መግባት አለብኝ፡፡“
“ታዲያ ምንድው ችግሩ?”
“አርባ ሺህ ብር ልሰጣት አልፈለግማ!”
“ለእሱ መፍቴውን ልንገርህ…”
“እባክህ ንገረኝ…”
“ልክ ሠላሳ አምስት ዓመት ሲሞላሽ አርባ ሺህ ብሩን እሰጥሻለሁ በላት፡፡ እሷ ሠላሳ አምስት ዓመት ሳይሞላት ሁለታችሁም ታረጃላችሁ፡፡”
አሪፍ አይደል!
እናላችሁ…አባቶቻችን ‘ሐሜተኛ ያፍራል፡ ሀሰተኛ ይረታል’ ይሏት የነበረችው አባባል ከተማችን ውስጥ የትራፊክ መብራቶች ባሉባቸውና በሌሉባቸው ስፍራዎች ሁሉ በትልቁ ተጽፋ ትለጠፍልንማ!
የሀሜት ‘ብሬኪንግ ኒውስ’ ከመሆን ያድነንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Saturday, 21 March 2015 10:08

የፀሐፍት ጥግ

ፀሐፊ፤ የበለጠ ገንዘብ እንዴት አገኛለሁ ሳይሆን ብዙ አንባቢያን ጋ እንዴት እደርሳለሁ ነው ማለት ያለበት፡፡
ብሪያን አልዲስ
 ታሪክ ፀሐፊ ይመዘግባል፤ ልብ ወለድ ፀሐፊ ይፈጥራል፡፡
ኢ.ኤ.ፎርስተር
በአርታኢዎች ወይም በሃያሲያን አስተያየት አትዘን፡፡ እነሱ የጥበብ ትራፊክ ፖሊስ ናቸው፡፡
ጊኒ ፎውለር
ግንብን በመሬት ላይ ከመገንባት ይልቅ በአየር ላይ መገንባት የበለጠ እርካታ አለው፡፡
ኢድዋርድ ጊቦን
ስለምታውቀው ነገር ከመፃፍ ይልቅ  ስለሚሰማህ ነገር መፃፍ የተሻለ ነው፡፡
ኤል.ፒ.ሃርትሌይ
ፀሃፊ ጨርሶ እረፍት የለውም፡፡ የፀሐፊ ህይወት አንድም መፃፍ ነው አሊያም ስለሚፅፈው ማሰብ ነው፡፡
ኢዩጂኔ ሎኔስኮ
ጠዋት እነሳለሁ፤ መተየቢያ ማሽኑን እስኪያቃስት ድረስ እቀጠቅጠዋለሁ፤ ከዚያ አቆማለሁ፡፡
ክላረንስ ቡዲንግቶን ኬላንድ
የምንፅፈው ስለፈለግን አይደለም፤ የምንፅፈው መፃፍ ስላለብን ነው፡፡
ሶመርሴት ሟም
ፀሃፊውን ያላስለቀሰ፣ አንባቢውን አያስለቅስም፡
ጆርጅ ሙሬ
ሥራው መናገር ሲጀምር ደራሲው አፉን መጠርቀም አለበት፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
 በትንሽ ድፍረት ማጣት ብቻ ዓለም ተሰጥኦዎችን ታጣለች፡፡
ሲድኒ ስሚዝ
የመጀመሪያው ምዕራፍ የአሁኑን መፅሃፍት ሲያሸጥ፣ የመጨረሻው ምዕራፍ ቀጣዩን መፅሃፍ ያሸጣል፡፡
ሚኪ ስፒላኔ
ሃያሲ መንገዱን የሚያውቅ ግን መኪና መንዳት የማይችል ሰው ነው፡፡
ኬኔዝ ቲናን
ለቃላት ድምፅ ትኩረት ስጥ፡፡
ዴቭ ዎልቨርተን
መፃፍ በወረቀት ላይ ማሰብ ነው፡፡
ዊሊያም ዚንሰር

Published in የግጥም ጥግ
Page 7 of 21