ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በጣም ጨካኝ ሹም ነበረ ይባላል፡፡ ይሄው ሹም በትንሽ በትልቁ ይቆጣል፡፡ ይገርፋል፡፡ ያስገርፋል፡፡ ሲያሻውም ይገድላል፡፡ አገር ይፈራዋል፡፡ ሰው ሲሽቆጠቆጥለት የማየትን ያህል የሚያስደስተው ነገር የለም፡፡
ወደ ቤቱ እንኳ በጊዜ ገብቶ ሚስቱ፤
“ዛሬ እንዴት ዋልክ?” ስትለው፤
“አንቺ ምን አለብሽ ሰው አትገርፊ፣
አታስገርፊ፣ አትገይ አታስገድይ
ቤትሽ ተኝተሽ ትበያለሽ፤ እኔ ላቤን አፍስሼ ያመጣሁትን ትቦጠቡጫለሽ!” ይላታል፡፡
“በነገራችን ላይ የአቶ እገሌ ልጅ ታሠረ ሲሉ ሰማሁ፡፡ አውቀሃል?”
“አዎን አውቄያለሁ፡፡ እኔ ሳላውቅ የሚሆን ነገር የለም አላልኩሽም?”
“ውይ ትንሽ ልጅ እኮ ነው፡፡ 15 ነው 16 ዓመቱ!”
“አዎ! እሥር ቤት እንዲቆይ ወሰንን”
“ምን ብላችሁ ወሰናችሁ?”
“ለአቅመ አዳም እስኪደርስ ይቀመጥና ሲያድግ እንገርፈዋለን ብለን ወስነናል”
“ውይ እንዴት ክፉ ናችሁ! አሁን ከእናንተና ከልጁ ማ ቀድሞ እንደሚሞት በምን ይታወቅና ነው እንዲህ የምትጨክኑት?”
“ስለ ነገ አርቀሽ ካላሰብሽ ምን ሠርተሽ ትኖሪያለሽ? ጠዋት የሆነውን ሳልነግርሽ? አንድ የህግ ት/ቤት ሄጄ ህግ መማር እፈልጋለሁ ብላቸው፤ ዲሬክተሩ አይቻልም!” አሉኝ
“ለምን አሉ?”
“አንተማ ፈርደህ ጨርሰሃል!” አሉኝ፡፡
“ይሄዋ እቅጩን ነገሩህ!”
“ዕውነትሽን ነው፡፡ ፈርጄ አለመጨረሴን ያሳየሁዋቸው አሁን እና እሥር ቤት ጐራ ብዬ ተሰናብቻቸው ስመጣ ነው!” ብሎ ሳቀ፡፡
                                         *    *    *
ሀገራችን ብዙ ለከት የለሽ ጭካኔ አይታለች፡፡ “ግፉ በዛብኝ እራሴን እገላለሁ” ያሉትን ተበዳይ፤ “እሱንም እኛ ከፈቀድንልህ ነው” ካሉት መሪ “ብዙ ቦታ አትፍጁ፤ አንድ ላይ ቅበሩ” እስካሉ መሪ ድረስ፤ ሰው ጤፉ ጭካኔ አይተናል/ታዝበናል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዘመናት የሚወራው ስለ ህዝብ ነው፡፡ ስለ ሀገር ሉዓላዊነት ነው፡፡ ስለ ሀገራዊነት ነው ስለ አንድነት ነው፡፡ ስለ ዕድገትና ብልፅግና ነው፡፡ የተሻለ ኢኮኖሚ ስለማምጣት ነው፡፡ ስለ ፍትሕ ርትዕ ነው፡፡ ህዝብ የፈለገውን መሪ እንዳገኘ ነው፡፡ ለውጥ በየቀኑ እየመጣ እንደሆነ ነው፡፡ ለውጥ ግን መሠረታዊ መሆን እንዳለበት በቅጡ የተናገረም፣ የተገበረም አልታየም፡፡
“ለውጥ አምፖል የመለወጥ ጉዳይ መሆኑ አብቅቷል፡፡ ይልቁንም ዓለምን ሙሉውን የመለወጥ፣ ሙሉን የማብራት ጉዳይ ነው” ትለናለች ናዎሚ ክላየን፡፡
አንድም አንድ አምፖል ቀይሮ መፎከር አሳሳች ስለሆነ፤ አንድም ደግሞ ቢያንስ የተሻለ አምፖል መሆን አለመሆኑ አለመታወቁም ነው፡፡ በመጨረሻም ዘላቂና አስተማማኝ ለውጥ ለማግኘት ለዋጩ ብቻ ሳይሆን ተለዋጩ ህዝብ ይሆነኛል ማለት ስላለበት ነው፡፡
ተጠቃሚውም አረጋጋጩ እሱ ነውና፡፡ ይህንን ህዝብ ተኮር መርህ ስንቶች ተመራጮች ከልባቸው አስበውበት፣ ምን ያህልስ ይታገሉለት ይሆን? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ በምርጫ ፉክክር ውስጥ አሯሯጭ የሚባል አለ እንዴ? የቅስቀሳ የአየር ጊዜ ምን ያህል የነገ ማንነትን ጠቋሚ ይሆን?
“ካልታዘልኩ አላምንም” ያለችው ሙሽሪት፣ ይፈረድባት ይሆን? እስከዛሬ ምን ያህል ያማሩ ፕሮግራሞችን አይተናል? እኒያን ፕሮግራሞች ስንቶች ከልብ ደከሙባቸው? ምን ያህል ህዝብ ልብ ውስጥ ገቡ/ኖሩ? የተቀሰቀስነውን ያህል ነቅተን ይሆን? ከጠዋቱ ጭቅጭቅ፣ ንትርክና፣ መፈነካከት ውስጥ መግባት በረከሰባት አገራችን ምን ያህል ተወዳዳሪ ይሳካለት ይሆን? ነው ወይስ ስትታጭ ያጣላች፤ በሠርጓ ታጋድላለች ይሆን አካሄዱ? እስቲ ለነገ ያብቃን ለፍሬ - ግብሩ!


Published in ርዕሰ አንቀፅ

ኢህአዴግ፣ ኢዴፓና መድረክ ርዕዮተ ዓለማቸውን ያቀርባሉ

      ዛሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ቤት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ  ኢህአዴግ፣ መድረክ እና ኢዴፓ በርዕዮተ ዓለማቸው ላይ መነሻ ፅሁፍ በማቅረብ ይከራከራሉ፡
ከሁለት ወር በኋላ ለሚካሄደው የግንቦቱ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው የፓርቲዎች ክርክር ላይ ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲን፣ ኢዴፓ የሊበራል ዲሞክራሲን እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የሶሻል ዲሞክራሲን ፅንሰ ሃሳቦችና መርሆዎች የተመለከቱ ፅሁፎች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ት/ቤት ዲን ዶ/ር አብዲሣ ዘርአይ፤ ሶስቱ የፖለቲካ ርዕዮተ አለሞች ለክርክር የተመረጡት አብዛኞቹ የሀገራችን ፓርቲዎች የእነዚህ ርዕዮተ ዓለም አራማጅ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
በዛሬው ክርክር በሊበራል ዲሞክራሲ ላይ መነሻ ሃሣብ እንዲያቀርቡ የተጋበዙት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ እንዲህ ያሉ የሃሣብ ማንሸራሸሪያ መድረኮች የፓርቲዎችን የፖለቲካ አማራጭ ለህዝብ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ፓርቲያቸው የሚከተለውን የሊበራል ዲሞክራሲ ርዕዮተ አለም ከኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድምታው አንፃር ለማብራራት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ምህዳር ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ቢኖርም ያገኙትን ራስን የማስተዋወቂያ አማራጭ ሁሉ አሟጠው መጠቀም ይገባቸዋል ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ ኢዴፓም አማራጭ ሃሣቦቹን ለህዝብ ለማድረስ ያገኛቸውን ዕድሎች በሙሉ ይጠቀማል ብለዋል፡፡
መድረክን ወክለው የሶሻል ዲሞክራሲን ርዕዮተ አለም በተመለከተ የመነሻ ሃሣብ የሚያቀርቡት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ እንዲህ አይነቱ መድረክ መዘጋጀቱ ለፓርቲዎች ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው በክርክር መድረኩ ላይ የሶሻል ዲሞክራሲ መርሆዎችን እንደሚያቀርቡና ከክርክሩ መልካም ነገር ይገኝበታል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
የኢህአዴግ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ደስታ ተስፋሁ በሰጡት አስተያየት፤ መራጩ ህዝብ በፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ እንዲረዳ መሰል መድረኮች አስፈላጊ መሆናቸው ገልጸዋል፡፡
በክርክሩ ላይ በተጋባዥነት ከተጠሩት ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ሠማያዊ ፓርቲ በርዕዮተ አለም ላይ ክርክር ከመደረጉ በፊት ምርጫው የሚካሄድበት ምህዳር መስፋት አለበት ብሏል፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ “በዚህ ሰአት መነጋገር የነበረብን የመድብለ ፓርቲ ስርአት አደጋ እየተጋረጠበት ስለመሆኑና የፖለቲካ ምህዳሩ ስለመጥበቡ እንዲሁም በፀረ ሽብር ህጉ ላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

የታዛቢነት ግብዣም ከመንግስት አልቀረበልኝም ብሏል

   የግንቦቱን ምርጫ ለመታዘብ ከመንግስት ግብዣ እንዳልቀረበለት የገለፀው የአውሮፓ ህብረት፣ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች በታዛቢዎቼ የቀረቡ ሪፖርቶች በኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት ማጣታቸውም ከታዛቢነት እንድርቅ ገፋፍቶኛል አለ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በ1997 እና 2002 ምርጫዎች የህብረቱን የትዝብት ሪፖርት ሙሉ ለሙሉ ሳይቀበለው መቅረቱ፤ ለዘንድሮ ምርጫ ሌላ የታዛቢ ቡድን የማሠማራትን ጥቅም አጣራጣሪ እንዲሆን አድርጓል ብሏል - የአውሮፓ ህብረት፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ የአውሮፓ ህብረት በታዛቢነት አለመሳተፉ በምርጫው ተአማኒነት ላይ የሚያወጣው ለውጥ የለም ብሏል፡፡
ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሣለኝ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የአውሮፓ ህብረት በራሱ ምክንያት ምርጫውን እንደማይታዘብ ማሣወቁን ጠቁመው፤ ምርጫውን የአፍሪካ ህብረት፣ የአገር ውስጥ ሲቪል ማህበራትና ተቋማት ይታዘቡታል ብለዋል፡፡
በአና ጐሜዝ የሚመራው የአውሮፓ ህብረት ታዛቢ ቡድን በ97 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ክፉኛ በመተቸቱ ከፍተኛ ውዝግብ ከመፈጠሩም በተጨማሪ፣ በ2002 ምርጫም ህብረቱ የምርጫው እለት ሂደቱ መልካም የነበረ መሆኑን ከገለፀ በኋላ፣ በጥቅሉ ምርጫው በአለማቀፍ መመዘኛዎች ሲፈተሽ ግን በርካታ ጉድለቶች አሉበት በማለት ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

     ዐድዋን ጨምሮ በተለያዩ ጦርነቶች በመዝመትና በነገሥታት መናገሻነቱ የሚታወቀው ታሪካዊው የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ባለዕዳ በሚያደርግ ከፍተኛ የገንዘብ ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ምንጮች ገለፁ፡፡
ደብሩ ‹‹ዳዊት ወንድሙ›› በተባለ የሕንፃ ሥራ ተቋራጭ በማሠራት ላይ የሚገኘው ባለአራት ፎቅ የንግድ ማዕከል ሕንፃ፣ በሰኔ ወር 2004 ዓ.ም. በውስን ጨረታ በወጣ ማስታወቂያ መሠረት በሰበካ ጉባኤውና በልማት ኮሚቴው ጥምር የጋራ ስብሰባ ለአሸናፊው ድርጅት ተወስኖ የኮንትራት ውሉም በብር 61‚234‚885.02 ጠቅላላ ወጪ ተፈጽሞ እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፤ አማካሪ ድርጅቱም የተቀጠረው በግልጽ አሠራር ተለይቶ መሆኑን፣ ተናግረዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የደብሩ አስተዳደር በዲዛይን ክለሳ ሰበብ የግንባታ ዋጋውን ከዕጥፍ በላይ በማናር የሥራ ውሉን መቀየሩ ተመልክቷል፡፡ የቀድሞውን አማካሪ መሐንዲስ በማሰናበትም ‹‹የዲዛይን ክለሳና ተያያዥ ሰነዶች ፍተሻ በማስፈለጉ›› በሚል ሰበብ ያለምንም ግልጽ መመዘኛና ውድድር በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በተቀጠረው ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ለተደረገው የፕላን ማሻሻያ 80‚500 ብር የተከፈለ ሲኾን የግንባታ ወጪውም ከ170 ሚልዮን ብር በላይ ከፍ ማለቱ ታውቋል፡፡
የኮንስትራክሽንን ሕጉን በመጣስ ያለጨረታ የተሰጠው ‹‹የፕላን ማሻሻያ››ና የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ በመተላለፍ ሀገረ ስብከቱ ባልፈቀደው ‹‹የተከለሰ ዲዛይን›› መቀጠሉ የተገለጸው ግንባታ፣ ከ80 ሚልዮን ብር ያላነሰ የወጪ ልዩነት ቢታይበትም እንደጭማሪ የተጠቀሱት የአሳንሰርና የኤሌክትሪክ ዝርጋታዎች የተጠቀሰውን ወጪ ምክንያታዊ እንደማያደርጉት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ሕንፃው ከጠቅላላ ሥራው በሢሦ ደረጃ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት  ወጪው ከ25 ሚልዮን ብር በላይ መድረሱ፣ ሥራው በማዕከል ከተፈቀደው ውጭና በተለየ ውል እየተካሔደ መኾኑን ያረጋግጣል ብለዋል - ምንጮቹ፡፡
የደብሩ ይዞታዎች በኾኑ ኹለት ሕንፃዎች ላይ ቅርንጫፎችን ለመክፈት የደብሩ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሜን አዲስ አበባ ዲስትሪክት ጋራ ያደረገው የኪራይ ውል የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ የጣሰ እንደኾነ የደብሩ ሠራተኞች ያስረዳሉ፡፡ የደብሩ አስተዳደር በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ከባንኩ ጋር በፈጸመው የዐሥር ዓመት የኪራይ ውል፣ የአቡነ ጴጥሮስ ቅርንጫፍ እና መሀል ፒያሳ ቅርንጫፍ ለመክፈት ብር 12 ሚልዮንና ብር 28 ሚልዮን በድምሩ ብር 40 ሚልዮን እንዲከፈለው መስማማቱ ታውቋል፡፡
መዋቅራዊ አሠራርንና የሌሎችን የሥራ ሓላፊነት በማናለብኝነት በመጣስ እየተፈጸመ ነው በተባለው የገንዘብ ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ዋነኛ ተጠያቂ የተደረጉት የደብሩ አስተዳዳሪ፣ የቢሮ ሠራተኞችንና ባለሞያዎችን በዛቻ ቃል በማሸማቀቅ እንደሚወቀሱ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የሕዝብ ሀብት የኾነችው ቤተ ክርስቲያን ‹‹በልማት እየተመካኘ ተገቢ ባልኾነ የሥራ ሒደት በዕዳ እንዳትዘፈቅ፣ የሠራተኛው የሥራ ዋስትናም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ›› ሲሉ ያሳሰቡት የደብሩ ሠራተኞችና ምእመናኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ታሪካዊውን ደብር የሚታደግ ፈጣንና ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ተማፅነዋል፡፡
ከመስከረም ወር 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የደብሩ አስተዳዳሪ በመሆን የተሾሙት መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃን ስለጉዳዩ በስልክ አነጋግረናቸው፤ ‹‹የምእመናን አቤቱታ እንድትቀበሉና ይህን ጉዳይ እንድትመረምሩ ሥልጣን የሰጣችኹ ማን ነው?›› በማለት በአካል ካልኾነ በቀር በስልክ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልኾኑ በመግለጻቸው ቀጠሮ ለመያዝ ስንሞክር ስልኩን ጆሮአችን ላይ በመዝጋታቸው ጥረታችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Published in ዜና

የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ መንግስታት ምላሽ አልሰጡም
የአሜሪካ መንግስት ዘገባው አስቂኝ አልቧልታ ነው ሲል አጣጥሎታል
ተጠርጣሪ ሆኖ የተጠቀሰው የሱዳን መንግስትም ዘገባው የውሸት ፈጠራ ነው ብሏል

     ከረዥም ጊዜ ውዝግብ በኋላ እ.ኤ.አ በ2012 የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙት ደቡብ አፍሪካዊቷ ዱላሚኒ ዙማ ላይ፣ በዚያው ሰሞን እዚሁ  አዲስ አበባ ውስጥ ግድያ ሊፈፀምባቸው ነበር በሚል አልጀዚራ ሰሞን ዘገበ፡፡
የግድያ ሴራው ጠንሳሾች ማንነትንና መነሻ ሰበቡን በግልጽ ያልዘገበው አልጀዚራ፣ ሱዳን ተጠርጣሪ እንደነበረች ጠቅሶ ሴራው ለደቡብ አፍሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ የደህንነት ሰዎች ድንገተኛ ነበር ብሏል፡፡
ከደቡብ አፍሪካም ሆነ ከኢትዮጵያ በኩል ዘገባውን በተመለከተ የተሰነዘረ ምላሽ የለም፡፡ የአፍሪካ ህብረትም፤ በአልጀዚራ የተላለፈውን ዘገባ አይተነዋል ከማለት ውጭ፣ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ምላሽ አልሰጠም፡፡
ኮሚሽነሯ የስራ ሃላፊነታቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ እያከናወኑ ናቸው በሚል መግለጫ ያወጣው የአፍሪካ ህብረት፤
የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ተቋም፤ የህብረቱ መሪዎችና ተወካዮችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያካሂደውን ስራ እናደንቃለን፤ እንደአስፈላጊነቱም ከደቡብ አፍሪካ መንግስትና ከሌሎች የህብረቱ አባል አገራት ጋርም በትብብር ይሰራል ብሏል፡፡
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ ሊንዳ ግሪንፊልድ ግን፣ ዘገባውን የሚያጣጥል ቀጥተኛ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የግድያ ሴራ ተጠንስሶ ነበር የሚለው መረጃ ከየት እንደመጣ አይታወቅም፤ ቁም ነገር የሌለው ቧልት ነው ብለዋል - ሃላፊዋ፡፡
በአልጀዚራ ዘገባ ውስጥ የግድያ ሴራ ተጠርጣሪ ሆኖ የተጠቀሰው የሱዳን መንግስትም፤ ዘገባው የውሸት ፈጠራ ነው በማለት እንዳስተባበለ ሱዳን ትሪቢዩን ገልጿል፡፡ የግድያ ሴራን የሚያክል ወንጀል ያለ ጠንካራ መነሻ ሰበብ እንደማይጠነስስ የገለፁ የሱዳን መንግስት ባለስልጣናት፤ “ኮሚሽነሯን ለመግደል ሱዳን ምን መነሻ ሰበብ ይኖራታል?” በሚል ዘገባው ጤናማ አእምሮ ላለው ሰው ትርጉም የሚሰጥ አይደለም ብለዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ መንግስት እና ኮሚሽነሯ በጉዳዩ ላይ ምንም አለማለታቸው አስገራሚ ነው ሲሉ፣ የሱዳን ባለስልጣናት መናገራቸውንም የሱዳን ትሪቡን ገልጿል፡፡

Published in ዜና

‹‹የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የፓትርያርኩን እገዳ ተቃወሙ›› በሚል ርእስ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የቀረበው ዘገባ የስም ማጥፋት ዘመቻ መኾኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ገለጸ፡፡
የአዲስ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጋራ በመተባበር የየአድባራቱን የሰንበት ት/ቤቶች የሥራ አመራር የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ሰብስቦ የማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስና የመምሪያው ምክትል ሓላፊ በተገኙበት የሥራ አመራር እንደሰጣቸው መምሪያው በደብዳቤው አስታውሷል፡፡ ይኹን እንጂ በጋዜጣው ላይ በቀረበው ዘገባ÷ ዓላማው በውል ባልታወቀ ኹኔታ፣ በወቅቱ ያልተባለና ኾን ተብሎ የተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ በአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አመራር ላይ እንደተፈጸመ በደብዳቤው አስታውቋል፡፡
ማደራጃ መምሪያው አያይዞም ‹‹የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የበላይ አመራርና የበታች አካላት ለማለያየት፣ ከዚህም ጋራ መንግሥታችን ለምርጫው በሰላም ዙሪያ በሚሠራበት ወቅት ሕዝብን ለመበጥበጥ እንዲሁም ወጣቱ የሰላም ተልእኮውን በአግባቡ እንዳይወጣ ለማድረግ›› ኾን ተብሎ እንደተቀነባበረ ገልፆ ‹‹የሃይማኖቱን ተከታዮች በእጅጉ አሳዝኖናል›› ብሏል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትና የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በዕለቱ ስላደረጉት የግማሽ ቀን ውይይት የስብሰባውን ተሳታፊዎች በምንጭነት በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

ተቀጣሪ ላልሆኑ 56 ወዳጅ ዘመዶቹ ደሞዝ ይከፍል ነበረ

      በደቡብ ክልል በስልጤ ዞን፣ ስልጤ ወረዳ፣ ቤተሰቦቹን ጨምሮ 56 የቅርብ ዘመዶቹንና ወዳጆቹን የመንግስት ተቀጣሪ በማስመሰል የደሞዝ መክፈያ መዝገብ ላይ አስፍሮ በየወሩ ደሞዝ በመክፈል የወረዳውን ሩብ ሚሊዮን ብር መዝብሯል የተባለው ተጠርጣሪ በፖሊስ እየተፈለገ ነው፡፡
የወረዳው የፋይናንስ ግዢና ክፍያ ሠራተኛ የነበረው ቢኒያም አካሉ የተባለው ተጠርጣሪ አባቱን፣ እህት ወንድሞቹንና ባለቤቱን ጨምሮ የስጋ ዘመዶቹን ስም ከተለያዩ የወረዳው ሠራተኞች ስም ጋር ቀላቅሎ በመመዝገብ፣ ከጥቅምት 2007 ዓ.ም ጀምሮ ደሞዝ ሲከፍላቸው እንደነበር ፖሊስ ደርሶበታል፡፡
መጀመሪያ ሁለት ግለሰቦችን ከግብርና ባለሙያዎች ዝርዝር ጋር በመቀላቀል ደሞዝ እንዲከፈላቸው ያደረገ ሲሆን በየወሩ የሰው ቁጥር እየጨመረ ለ56 ሰዎች መንገድ በተመሳሳይ ደሞዝ ያስከፍላቸው እንደነበር የፖሊስ መረጃ ይጠቁማል፡፡
ተጠርጣሪው ገንዘቡን በዳሽን ባንክ ያስገባ እንደነበር የጠቆመው ፖሊስ፤ ሲደረስበት ገንዘቡን ከባንኩ አውጥቶ መሰወሩን ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪው ለህገወጥ የደሞዝ ክፍያ ይጠቀምባቸው የነበሩ ሠነዶችን ፖሊስ ያገኘ ሲሆን ግለሰቡን ለመያዝ ፎቶግራፉ እንደተሰራጨ፣ ከሃገር እንዳይወጣ የእግድ ትዕዛዝ መተላለፉንና ጠንካራ ፍለጋ እየተከናወነ መሆኑን የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር አብዱ አደም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡  
የወረዳው ፖሊስ የተጠርጣሪውን ወላጆች ጨምሮ 10 በግብረአበርነት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ለምርመራ 10 ተጨማሪ ቀናት መጠየቁንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ዜና

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ከ2 ቢ. ብር በላይ ፈጅቷል
 ፋብሪካዎቹ በአገር ውስጥ ገበያ መገደብ የለባቸውም ተባለ

የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰራው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሰሞኑን የተመረቀ ሲሆን ማስፋፊያው የፋብሪካውን የማምረት አቅም በሶስት እጥፍ እንደሚያሳድገው ተገለጸ፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት በ225 ሚሊዮን ዶላር ዲያጆ ለተባለ የፈረንሳይ ኩባንያ የተሸጠው  የሜታ አቦ ቦራ ፋብሪካ ከትናንት በስቲያ ያስመረቀው አዲሱ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በዓመት 550 ሺ ሄክቶ ሊትር የነበረውን የፋብሪካውን የማምረት አቅም ወደ 1.7 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ከፍ ያደርገዋል ተብሏል፡፡  
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢንፎርሜሽንና መገናኛ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የተመረቀው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትሩ ዶክተር መብራቱ መለስ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤አገሪቱ በምትከተለው ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋትና የግብርና ኢንዱስትሪን የማስተሳሰር ተግባር ላይ ፋብሪካው ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የኢንፎርሜሽንና መገናኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ ፋብሪካው የተማረውን የሰው ኃይልና በግብርና ስራ ላይ የተሰማራውን ዜጋ በእኩል አገጣጥሞ የስራ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመው በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ሰዎችን ከማሰማራቱም  በላይ ለአርሶ አደሩም ገበያ እንደፈጠረለት ተናግረዋል፡፡  
መንግስት ለፋብሪካ ግብአታቸው የግብርና ውጤቶችን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ እያበረታታና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤በሂደት እየታየ ማበረታቻውና ድጋፉ ሊቀነስና ሊቀር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ የቢራ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን በአገር ውስጥ ብቻ በመሸጥ ተገድበው መቅረት የለባቸውም ያሉት ሚኒስትሩ፤ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ አገር እንዲልኩ ግፊት ይደረጋል ብለዋል፡፡ አብዛኞቹ ቢራ አምራቾች በአገር ውስጥ በቂ ገበያ ስላላቸው ወደ ውጪ መላክ አይፈልጉ ይሆናል፤ነገር ግን ሁኔታው በዚህ መልኩ መቀጠል አይገባውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡  
“ከቢራ በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ አምራች ኩባንያዎች ወደ አገራችን እንዲመጡ እንፈልጋለን፡፡ እነሱን ማበረታታትና መደገፍ በጣም ያስፈልገናል፡፡ በቢራ ምርቶች ላይ ያለውን ጉዳይ ቀስ እያልን ጊዜ ወስደን ማየት ይገባናል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ በቂ ነው ብለን ለማቆም ባንችልም የተወሰኑ አማራጮችን ስናገኝ ድጋፍና ማበረታቻዎቹን እየቀነስን እንሄዳለን” በማለት አስረድተዋል፡፡ በቢራ ምርት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ኩባንያዎች እንዳሉ የጠቆሙት ዶ/ር ደብረፅዮን፤ እነሱም ገፍተው ሲመጡ የምናየው ይሆናል ብለዋል፡
የግማሽ ክ/ዘመን እድሜ ያስቆጠረው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ፣ በ1959 ዓ.ም ተመስርቶ ሥራ ሲጀምር በዓመት 50ሺ ሄክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም የነበረው ሲሆን በቅርቡ ማልታ ጂኒየስና ዘመን ቢራ የተባሉ  አዳዲስ ምርቶቹን ለገበያ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡  

Published in ዜና

    በአለም ባንክ እና በሌሎች አለማቀፍ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው በሚል የባንኩ የውስጥ መርማሪ ቡድን ያወጣውን ሪፖርት ባንኩ በትኩረት ተመልክቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጠው ሂውማን ራይትስ ዎች ጠየቀ፡፡
ባንኩ በበኩሉ፤ መርማሪ ቡድኑ ባወጣው ሪፖርት ላይ የተጠቀሱ ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች በር የሚከፍቱ በርካታ የአሰራር ችግሮች እንደሌሉበት ገልጾ፣ ጥናቱ እንደገና ሊከለስ ይገባል ብሏል፡፡ የአለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የመርማሪ ቡድኑን ሪፖርት ለመገምገምና የማኔጅመንቱን ምላሽ ለማሰማት በትናንትናው ዕለት ስብሰባ አድርጓል፡፡
ሂውማን ራይትስ ዎች ለአለም ባንክ የአፍሪካ ምክትል ፕሬዚደንት በላከው ደብዳቤ እንዳለው፣ የባንኩ ገለልተኛ የተጠያቂነት ስልት መርማሪ ቡድን በጉዳዩ ዙሪያ ባደረገው ምርመራ በኢትዮጵያ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ ተግባራዊ የሚያደርገውን የራሱን ፖሊሲ እንደሚጥስ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ቡድኑ ባለፈው ወር ባወጣው ሪፖርት፤ በአለም ባንክ ፕሮጀክቶችና በኢትዮጵያ መንግስት የመልሶ ማስፈር ፕሮግራም መካከል የአሰራር ግንኙነት እንዳለ ማረጋገጡንና ይህም የአለም ባንክ ለነባር ህዝቦች መብቶች መከበር የቆመውን የራሱን ፖሊሲ እየጣሰ እንደሚገኝ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ማስታወቁንም አክሎ ገልጧል፡፡
መርማሪ ቡድኑ መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማስፋፋት ዓላማ ያላቸውንና በአለም ባንክ፣ በእንግሊዝ መንግስት የአለማቀፍ ልማት ድርጅት፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በሌሎች ለጋሾች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ፕሮጀክቶች በተመለከተ ከጋምቤላ ክልል ስደተኞች የቀረበለትን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ባደረገው ማጣራት፣ የአለም ባንክ በፕሮጀክቶቹ ውስጥ ለሚታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰት አደጋዎች ይህ ነው የሚባል ትኩረት እንዳልሰጠ ማረጋገጡን የሂውማን ራይትስ ዎች አለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ጀሲካ ኢቫንስ ገልጸዋል፡፡
የአለም ባንክ በኢትዮጵያ የሚያከናውናቸውን ፕሮጀክቶች አካሄድ ማስተካከል የሚችልበት ዕድል አለ ያሉት ጀሲካ ኢቫንስ፣ ባንኩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሰለባ የሆኑ ስደተኞችን የመብቶቻቸው ተጠቃሚ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል፡
ኢትዮጵያ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች በማሳካት ረገድ አበረታች ውጤት ማስመዝገቧ፣ አገሪቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ እና የአገር ውስጥ ገቢ እድገት እያሳየች መሆኗን ያመላክታል ያለው የእንግሊዝ መንግስት በበኩሉ፣ ይህም የአገሪቱን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ የሚሰጠውን እርዳታ ከመሰረታዊ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ስራ ፈጠራና ራስን የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ለማዞር እንዳነሳሳው ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡ የእግሊዝ መንግስት የእርዳታ አቅጣጫ ለውጡ ለኢትዮጵያ በሚሰጠው የገንዘብ መጠን ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድርና በኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጹን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ለእንግሊዝ መንግስት ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡

Published in ዜና

*በርካታ የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ይሳተፉበታል

ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ የፊታችን ሰኞና ማክሰኞ ትምህርታዊ ፌስቲቫል ያካሄዳል፡፡ “የትምህርት እድልን በተቀናጀ መንገድ ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተማሪዎችን ማገናኘት” በሚል መሪ ቃል በሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ በሚካሄደው ትምህርታዊ ፌስቲቫል ላይ በርካታ የውጭ ዩኒቨርስቲዎች እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የአሜሪካው ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲና ፍራንክሊን ዩኒቨርሲቲ፣ የህንዱ አቻርያ ኢንስቲቲዩት፣የቱርኩ ኦካን ዩኒቨርሲቲ፣ የካናዳው ብሮንስቶን አካዳሚ፣ የማሌዢያው ማሌዢያ የትምህርት ማዕከል፣ የጣሊያኑ ካቶሊካ ዩኒቨርሲቲ፣ የኡጋንዳው ቪክቶሪያ ዩኒቨርሲቲ፣ የስዊዘርላንዱ ሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ የቆጵሮሱ ግሪኒ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ፣ የደቡብ አፍሪካው ጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገኙበት የኮሌጁ የሚዲያ አስተባባሪ አቶ ቶፊቅ ሁሴን ገልጸዋል፡፡
በሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ አስተባባሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ትምህርታዊ ፌስቲቫል ቀጣይነት እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን የሌሎች አገራት ዩኒቨርሲቲዎችም በየተራ ፌስቲቫሉን ያዘጋጃሉ ተብሏል፡፡ የፌስቲቫሉ ዋና ዓላማ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና ተማሪዎችን በማገናኘት ልምድ ማለዋወጥና በስኮላርሺፕ ሂደት ላይ ደላሎች የሚሰሩትን አሻጥር በማስቀረት፣ የየአገራቱ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርታቸው ብልጫ ላላቸው ተማሪዎች በቀጥታ የትምህርት እድል እንዲሰጡ ለማድረግ እንደሆነ አቶ ቶፊቅ ተናግረዋል፡፡  
የፊታችን ሰኞና ማክሰኞ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት እስከ 11 ሰዓት በሚካሄደው ፌስቲቫል፤የአገራችንም ዩኒቨርሲቲዎች የሚሳተፉ ሲሆን ፌስቲቫሉ አገራችን ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት የምታደርገውን ጥረት በማገዝ በእውቀት የበለፀገ ማህበረሰብን ለማፍራት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ላይ የልምድ ልውውጦች፣ የፓናል ውይይቶችና መሰል ዝግጅቶች የሚካሄዱ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በስፍራው ተገኝተው እንዲጎበኙት ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ጋብዟል፡፡

Published in ዜና