Monday, 02 March 2015 09:35

ታላቁ የአድዋ ድል

“የዓለም ታሪክ ተገለበጠ”

ከፈረሠኞች አሉ በልዩ
መሀል አገዳ የሚለያዩ፤
*   *   *
አየሁት አድዋን እንደ ኮከብ ደምቆ
የበቀለበትን ሠው መሬት ላይ ወድቆ፤
*   *   *
የአድዋ ሥላሤን ጠላት አረከሠው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሠው፤
*   *   *
ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ
ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ፤
*   *   *
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፤
*   *   *
ታላቁ የአድዋ ጦርነት የአፍሪቃውያን ትውልዶች ታላቅ የነፃነት ተጋድሎ ነው፡፡ ሞትና ባርነት የተቀበሩበት፤ እውነትና ፍትህ አሸንፈው ህይወት የዘሩበት፡፡
ልክ የዛሬ አንድ መቶ አሥራ ዘጠኝ ዓመት፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም “ጥቁር ህዝብ ትልቅ ትል ነው ቅንቡርሥ ነው እንጂ ነፍሥ ያለው ሠው አይደለም” ብለው አፍሪቃን በሽሚያ የተቀራመቱ የአውሮጳ ቅኝ ገዢዎች ከመላው ኢትዮጵያ ዳር እስከዳር ተወጣጥቶ አድዋ በዘለቀ አንድ መቶ ሺህ የገበሬ ሠራዊት የተቆጣ ክንድ አድዋ ላይ ድባቅ ተመቱ፡፡
እንግሊዞች ፡- የዓለም ታሪክ ተገለበጠ፤ ታላቅ የትውልድ ኃይል አፍሪቃ ውስጥ ተቀሠቀሠ…አሉ፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ፤ “ኢትዮጵያውያን ባበደ መንፈሥ ተዋግተው የአውሮጳን ቅኝ ገዢዎች አሸነፉ”…በማለት ፅፈዋል፡፡
በመቶ ሺህ ከሚሠላው የገበሬ ሠራዊት ሃያ ዘጠኝ ሺህ የሚሆነው ፈረሠኛ ነው፡፡ በአድዋ ገመገሞች ፡- በረቢ አርእየኒ በሸልዶ ተራራ በማርያም ሸዊቶ…የሚያብረቀርቅ ጐራዴያቸውን አየር ውስጥ እየቀዘፉ፣ የጋሻቸውን እምብርት ምድር ላይ እያጠቀሡ ሠማይ ደርሠው ምድር እየተመለሡ ከሚያሽካኩ ሠንጋ ፈረሶቻቸው ጋር እየፎከሩ እየሸለሉ….ያበጠውን የአውሮጳ ኃይል የዶጋ አመድ አደረጉ፡፡ ከሌሊቱ በዘጠኝ ሠዓት ግድም የመጀመሪያዋ ጥይት ፈነዳች፡፡ የመጀመሪያዋ ጥይት የፈነዳችው ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሠዓት ግድም ነው የሚሉ የታሪክ ሊቃውንትም አሉ፡፡
በቅዱሥ ጊዮርጊስ በዕለቱ ቀኑ ማልዶ የተጀመረው ከባድ ጦርነት ከቀኑ አምሥት ሠዓት አካባቢ አሸናፊውን ወይንም ድል አድራጊውን ኃይል ለየ፡፡ በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነው የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ሠራዊት ከኢትዮጵያ የተቆጣ ጀግና የገበሬ ሠራዊት ጋር ግማሽ ቀን እንኳን በመተጋተግ ለመዋጋት አልቻለም፡፡ ከቀትር በፊት በጄኔራል ባራቴሪ የሚመራው አውሮጳዊ ሠራዊት ተፍረከረከ።
ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ ያለቀው አልቆ፣ የቆሰለው ቆሥሎ የተረፈው መሸሽ ሲጀምር ኢትዮጵያውያን ጀግኖች እያሣደዱ ፈጁት፡፡ ከሚሸሹት መሃከል አንዱ ጄኔራል ባራቴሪ ነው፡፡ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተማርኳል፡፡ ሃምሣ ስድሥቱም የኢጣሊያ መድፎች በኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት ተማርከዋል፡፡ አብዛኞቹ የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ወታደሮች ተገድለዋል፡፡ ጥቂቶቹ ከጄኔራል ባራቴሪ ጋር ሸሽተው ከማምለጣቸው በቀር ከሞት የተረፉት ቆሥለዋል፤ ተማርከዋል፡፡
የምርኮ ጓዙን ወደ አዲስ አበባ ለማጓጓዝ አምሥት መቶ አጋሠሥ አስፈልጓል፡፡ የኢጣሊያ ኮሎኒያሊስት ቁስለኞችን በማከምና በመርዳት፣ ምርኮኞችን በመመገብና ውኃ በማጠጣት እቴጌ ጣይቱ ብርቱ ኃላፊነት ተወጥተዋል፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከምሽቱ አራት ሠዓት ላይ ድል አድራጊው የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት እንዳማርያም (ቅድሥት ማርያም ቤተ ክርስቲያን) ተሠባሥቦ፣ በአንድ እግሩ ቆሞ ቀኙን የሠጠውን (ድል እንዲያደርግ የረዳውን) አምላክ አመሠገነ፡፡
በማግሥቱ የካቲት 24 ቀን 1888 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሠዓት ላይ ምርኮኞች በዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ ድንኳን አጠገብ እንዲያልፉ ተደረገ፡፡ ምርኮኞቹ ሲያልፉ በቆራጥ አፍሪቃዊ የገበሬ ጄኔራሎች የተመራው የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች ሁሉ እየፎከረ እየሸለለ አሣለፋቸው፡፡ ከሚፎክሩትና ከሚሸልሉት አንዱ ፈረንሣዊ የጦር መሣሪያ ጠጋኝ ኦርዲናንስ ካፒቴን ነው፡፡
የኢጣሊያ ምርኮኞች ለአገራቸው ምድር ከበቁ በኋላ ጄኔራል አልቤርቶኒ በፃፈው መፅሐፍ ላይ…”እየፎከሩ እየሸለሉ ከነበሩት ጥቁር አፍሪቃውያን መሀከል አንዱ እንደኛው አውሮጳዊ ፈረንጅ ነው”…ብሎአል፡፡ ከአገሩ ከፈረንሣይ ለጦር መሣሪያ ጥገና ሥራ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ይህ ፈረንሣዊ ካፒቴን ኦርዲናንስ “አሁን ጊዜው የጦርነት ስለሆነ ወደ አገርህ ተመለሥ” ቢሉት ቢሠሩት አሻፈረኝ ብሎ ከእኛ ጋር አድዋ ድረስ የዘመተ ነው፡፡
አድዋ ላይ የተዋጋንባቸው ሠማንያ ሺህ አሮጌ ጠመንጃዎች በምሥጢር የተገዙትም ከፈረንሣይ አገር ነው፡፡ አርመናዊ የትውልድ ሥረ መሠረት ኢትዮጵያዊ መንፈሥና ነፍሥ ያላቸው ሠርኪሥ ቴሪዝያን፤ አሮጌዎቹን ሠማንያ ሺህ ጠመንጃዎች ከአውሮጳ ወደ አፍሪቃ አሻግረው በጂቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ያሥገቡ ነጭ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡትም እኒህ ፅኑዕ የኢትዮጵያ ወዳጅና ነጭ ኢትዮጵያዊ ሠርኪስ ቴሪዝያን ሲሆኑ፡- ካስገቧቸው መኪናዎች አንዱ በአሁኑ ጊዜ አምስት ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ለላንቲካ ቆሞ ይታያል፡፡ “እንደ ሰርኪስ ባቡር” ተብሎ የተዘፈነው ስለዚህ ነው፡፡
 በአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያ የአውሮጳ ወራሪዎችን ያሸነፈችው በዋናው ወታደራዊ ውጊያ ብቻ ሣይሆን፤ ጥበብና ብልሀት በተመላ የአገር አስተዳደር ፖለቲካ የበላይነት - በወታደራዊ መረጃ ብልጫ  እና በሥልጡንና በበቃ ዲፕሎማሲያዊ አሠራር ጭምር ነው፡፡
ከሁለት መቶና ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት፡- የሶስት ማዕዘን ንግድ (Triangular Trade) በሚባለው የታሪክ ምዕራፍ፤ አውሮጳውያን ገዢዎች ጥቁር አፍሪቃውያንን በሠንሠለት አስረው እንደ ከብት እየነዱ በሴኔጋል በኩል ጐሬ ደሴት ላይ ያደርሷቸዋል፡፡ ሠባ ኪሎ ግራም ከመዘኑ ጥርሥና ጡታቸው ጤናማ ከሆነ፣ ወደ አሜሪካና ወደ ካሪቢያን ያሻግሯቸዋል፡፡ ይህንን መመዘኛ ካላሟሉ ለባህር አውሬ ይጥሉዋቸዋል፡፡ ጐሬ ደሤት ላይ እነዚያ ቁምጥማጭ ሠንሠለቶች ከዘግናኝ ትዝታዎቻቸው ጋር ዛሬም ድረሥ አሉ፡፡ ገዢዎቹ እያደር ለምን ጉልበታቸውን ብቻ አገራቸውንና ሀብታቸውን ጭምር ለምን አንዘርፍም ብለው ያሠቡ ይመስላል፡፡
ስለዚህ ነው በ1880ዎቹ መጀመሪያ ግድም ጀርመን አገር በርሊን ከተማ የተሠባሠበው የአውሮጳ ኮሎኒያሊስት ጥምር ኃይል አፍሪቃን በሽሚያ ለመቀራመት የወሠነው፡፡ ዕድል ከተባለ፤ እንዳለመታደል ሆኖ ለኢጣሊያ እኛ ደረሥነው፡፡
ቢያብጥ ቢደነድን ቢከመር እንደ ጭድ
ደንዳናውን እንዶድ ይቆርጠዋል ማጭድ፤
ያንን ለአያሌ መቶ ዓመታት ሲጠራቀም የኖረ እብሪትና እብጠት አድዋ ላይ በተንነው፡፡  ጥቁር ህዝብ ትልቅ ትል ቅንቡርሥ ሣይሆን ነፍሥ ያለው ሠው ከሠውም ሠው,ኧ ጀግና መሆኑን አድዋ ላይ ለዓለም ሁሉ ያሣየነው እኛ ነን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን።
ታላቁ የአድዋ ድል፤ በዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና አስደንጋጭ ለውጥ አምጥቶአል፡፡ ልክ እንግሊዞች እንዳሉት፡- “የዓለም ታሪክ ተገለበጠ! አዲስ የትውልድ ኃይል አፍሪቃ ውስጥ ተቀሠቀሠ፡፡
ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ በአካል ባልተገኙበት የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ታላላቅ የአፍሪቃ የጐሣ መሪዎች ጉባኤ ላይ የነፃነት ተጋድሎውን እንዲመሩ ሊቀመንበር ተደርገው ተመረጡ፡፡ የኢጣሊያው ንጉሥ ኢማኑኤል ኤምቤርቶ የልደት ቀን የሀዘን ቀን እንዲሆን ተወሠነ፡፡ ጄኔራል ባራቴሪ ጦር ፍርድ ቤት ቀርቦ ማዕረጉ ተገፈፈ፡፡ ፍሎሬንስ ሚላን ሮም ናፖሊ…የተሠኙት የኢጣሊያ ከተሞች በመንግሥታቸው ላይ በተቆጡ “ምኒሊክ ለዘላለም ይኑር” የሚል መፈክር ባነገቡ ሠልፈኞች ተጥለቀለቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ፡፡ በየአገራቱ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎዎች በቁጣና በኃይል ተቀሠቀሡ…
ለአድዋ ጦርነ መነሻ የሆነው የውጫሌ ውል አንቀፅ አሥራ ሠባት ነው፡፡
ከአዲስ አበባ በስተሠሜን ወደ ወሎና ትግራይ ስንሄድ,ኧ ከደሴ ከተማ አለፍ ብሎ ውጫሌ ከተማ ልንደርስ ስንል በስተግራ በኩል ከአምባሠል ተራራ ግርጌ ንጉሥ ይሥማ የሚባል ቦታ አለ፡፡ ከአድዋ ጦርነት በፊት የኢትዮጵያ መሪዎችና ቆራጥ የገበሬ ጄኔራሎች በዚህ ሥፍራ ነበሩ፡፡ የውጫሌ ውል የተደረገው እዚህ ቦታ ነው፡፡ የውሉ አንቀፅ አሥራ ሠባት የአማርኛ ቅጂ፡- “ኢትዮጵያ ከአውሮጳ መንግሥታት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት በኩል ማድረግ ይቻላታል” ሲል፤ የጣሊያንኛ ቅጂው ደግሞ ፡- “ኢትዮጵያ ከአውሮጳ መንግሥታት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት በኩል ማድረግ አለባት” ይላል፡፡ አማርኛው ፡- ከፈለገች…የሚል ሥሜት ይሠጣል፡፡ ኢጣሊያንኛው፡- ኢትዮጵያ ብትፈልግም ባትፈልግም ከሌላው አገር ጋር በኛ በኩል ነው መገናኘት ያለባት…ነው የሚለው። የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሣይሆን ልዕልናዋን ይነካል፡፡…ተገዙ፤ ለኢጣሊያ ተንበርከኩ!...ዓይነት መንፈስ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መሪዎች ለኢጣሊያው መልዕክተኛ የአንቀፅ አሥራ ሠባትን የኢጣሊያንኛ ቅጂ አስተካክል አሉት፡፡ በጅ አልል አለ፡፡
ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ ለጦርነት በተሠናዳ ልብ ንግሥት ባለቤታቸውን፡- “ጣይቱ መዘግየት አደገኛ ነው”…..አሉ፡፡ ጦርነት የግድ እና አይቀሬ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የኛ መሪዎች ጥበብና ብልሀት በተመላ የፖለቲካ አስተሣሠብ የኢጣሊያን ሸፍጥና ትንሽነት በልጠው ተገኙ፡፡
ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ድል የተቀዳጀችው ውጫሌ ላይ በፖለቲካ ነው፡፡ ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ ክተት አወጁ፡፡ መላው ኢትዮጵያ ዳር እስከ ዳር ተነቀነቀ፤ ተነቃነቀ፡፡
አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ ተጉዞ አድዋ ግድም እሚገኙ ገመገሞች የዘለቀው ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆን የተቆጣ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት የውጊያ መንፈሡ ሣይቀዘቅዝ አገልግሉ ሣይቀል…በፍጥነት ጦር መግጠም አለበት፡፡ ፈጥኖ ወደ ውጊያ መግባት፡፡ በፍጥነት ጦር ለመግጠም ፡- ወይ የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ሠራዊት ወደኛ መምጣት አለበት፤ ወይንም ደግሞ እኛ ወደ ቅኝ ገዢዎቹ ምሽግ መሄድ አለብን፡፡ ወደነሡ ምሽግ መሄድ የሚያስከትላቸው ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሁናቴዎች አሉ፡፡ ለምሣሌ ምሽግ ላለ አንድ ወታደር የሚመጠነው ሶስት አጥቂ ወታደር ነው፡፡ ሶስት ለአንድ፡፡ ከምሽግ መውጣት ብዙ መስዋዕትነት ያስከፍላል፡፡ የግድ ከሆነ ግን የግድ ነው፡፡
ባሻዬ አውአሎም ሀረጐት ኢንቲጮ አካባቢ የተወለዱ ኢትዮጵያዊ ጐልማሣ ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት ምሽግ ተጠሩና ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነትና አደራ ተቀበሉ፡፡ ከእሣቸው ጋር ሌሎች ለኢጣሊያ መንግሥት የሚሠልሉ የኤርትራ ተወላጆች ፌርማቶሪዎች ባሉበት፡- በኢትዮጵያ ሠራዊት ውሥጥ የተሥቦ በሽታ መግባቱ፤ ሠራዊቱ ቀለብ መጨረሡ…በይፋ ተለፈፈ፡፡ ይሄንኑ እነባሻዬ አውአሎም የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ሠራዊት ወደሠፈረበት ቀጠና ዘለቁና የሆነውን ሁሉ ለጄኔራል ባራቴሪ ነገሩት፡፡ “ተስቦ በሽታ ገብቷል…ቀለብ አልቋል…፤ ስለዚህ፡- ጊዜው አሁን ነው” ብለው የልብ ልብ ሠጡት፡፡
ጄኔራል ባራቴሪ የካቲት 21 ቀን 1888 ሠራዊቱን እንዳያንቀሣቅስ ዝናብ ያዘው፡፡ በማግሥቱ የካቲት 22 ማምሻውን በጥድፊያ ተንቀሣቅሶ ወደ አድዋ ገሠገሠ፡፡ በባሻዬ አውአሎም ሀረጐት እየተመራ አድዋ ግድም እሚገኙ ጉድባዎች ጋ እንደደረሡ፣ ሊነጋጋ ሢል አውአሎም ቱር ብለው መሮጥ ጀመሩ። ባራቴሪ፡ “አውአሎም! አውአሎም!” ብሎ ተጣራ፡፡ “ግሥ! እስሀ ዝዋልካዬ አያውለና” (ወግድ! ዛሬ እኔ አንተን አያድርገኝ) ብለው ዘለው ራሥ አሉላ አባ ነጋ ምሽግ ገቡ፡፡ ባራቴሪና ወራሪ ሠራዊቱ በኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት በተቆጣ የእሣት አፍ ውሥጥ መሠሥ ብሎ ገባ፡፡ ወራሪው የአውሮጳ ጦር በጥቁር አፍሪቃዊ የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል የእሣት ላንቃ ውሥጥ ተመሠገ፡፡ ጣሊያኖች ድል የተነሡት በዚህ መልኩ ነው፤ በወታደራዊ ሣይንሥ የመረጃ ብልጫ፡፡
የኢጣሊያ ምርኮኞችና የምርኮው ጓዝ ከብዙ ቀናት ጉዞ በኋላ አገሪቱ ርዕሠ መዲና አዲስ አበባ ደረሠ፡፡ በአውሮጳ የኢጣሊያ ሹማምንት፡- “ኢትዮጵያውያን ያልሠለጠኑ አረመኔዎች ስለሆኑ ምርኮኞቻችንን ይገድላሉ፣ ያሠቃያሉ ብልቶቻቸውን ይቆርጣሉ”…እያሉ የኢትዮጵያን ሥም ያጐድፋሉ። ኢትዮጵያ ሁለት ትጉህና ብልህ ዲፕሎማቶቿን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ወላጅ አባት ራሥ መኮንን ጉግሣን እና ግራዝማች ዮሴፍን አውሮጳ አህጉር አስቀምጣ የኢጣሊያን ሹማምንት ሥም ማጥፋት ትመክታለች፡፡ ግራዝማች ዮሴፍ፤ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሣይኛና በኢጣሊያንኛ…እየተረጐሙ የኢትዮጵያንና የመንግሥቷን አቋምና አድራጐት ለዓለም ሁሉ ግልፅ ያደርጋሉ፡፡
በመጨረሻ ኢትዮጵያ የኢጣሊያን ምርኮኞች ግብር አብልታ አሥጨፍራ አሥደንሣ በጅቡቲ በኩል ወደ አገራቸው ወደ ኢጣሊያ በላከች ጊዜ፣ የኢጣሊያ ሹማምንት የኢትዮጵያን ሥም የማጉደፍ ዲፕሎማሲያዊ የቅጥፈት ዘመቻ እርቃኑን ቀረ፡፡ ጣሊያኖችን ለአራተኛ ጊዜ በለጥናቸው፡፡ በፖለቲካ ብልሀት፤ በዋናው የጦር ጐራ ወታደራዊ ግጥሚያ፤ በወታደራዊ መረጃ ብልጫ እና በዲፕሎማሲ…በልጠን አሸነፍናቸው፡፡
ታላቁ የአድዋ ድል!!
ታላቁ የአድዋ ድል፡- የኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን የመላው አፍሪቃውያን ክብርና ኩራት ነው፡፡ የኢትዮጵያና የአፍሪቃ ብቻ ሣይሆን የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦችና የመላው ዓለም የእውነትና የፍትህ ወገኖች ሁሉ ክብርና ኩራት ነው፡፡
አየሁት አድዋን እንደ ኮከብ ደምቆ
የበቀለበትን ሠው መሬት ላይ ወድቆ፤
ብሎ የገጠመው መዝገበ ጥበብ የምለው ኢትዮጵያዊው ሠዓሊና ገጣሚ መዝገቡ ተሠማ ነው፡፡
ይሄ ፅሁፍ ለጀግኖች አባቶቻችን ክብር፤ ለጀግኖች ወላጆቻችን ክብር …የተሠዋ ይሆን ዘንድ በመደነቅ ተበርክቶአል፡፡ ለክብራቸው ይቁምልኝ፡፡
ሠላምዎ ይብዛ! በፍቅር!
Soli-Deo.Gloria!

Published in ህብረተሰብ

ይበልጣል ይበልጣል ነው፤ ምልክቱም (›)
ያንሳልም ያንሳል ነው፤ ምልክቱም (‹)
እኩል ነውም ራሱን የቻለ ነው፤ ምልክቱም (=)
የ“ግን” ጉዳይ ግን ሌላ ነው፡፡ ይበልጣል “ግን” እዚህ ጋ ደግሞ ያንሳል፡፡ ያንሳል “ግን” እዚህ ነጥብ ላይ ግን ማነሱን በልጦታል፡፡ ይኼ ነው የዘንድሮው እውነታ ወለፈንድነት፡፡ ወለፈንድነቱ ራስ ምታት ሆኖብኛል፡፡ የራስ ምታቶቼን አይነት በምሳሌ ማሳየት ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ “ግን” ምን ዋጋ አለው?  ምሳሌ ቢበዛ መፍትሄ አይገኝ፡፡ መፍትሄ ቢገኝስ? … መፍትሄ ቢገኝም ግን እኔ ማማረሬን አላቆምም፡፡
ማሳያ አንድ፡- ብሔራዊ ትያትር ቤት
(የትያትር ዋጋ ከ15 ብር ወደ 40 ከመሸጋገሩ በፊት የተፃፈ)
የትያትር ቤት መግቢያው ሰዓት እኔ በበሩ እያለፍኩ ከነበርኩበት ቅፅበት ጋር ባይገጣጠሙ ኖሮ “ባቢሎን በሳሎን”ን ገብቼ ባልታደምኩ ነበር፡፡ ትያትር ቤት መንፈሳዊ ቦታ መሆኑን ከዚህ ቀደም በአርቲስት አንደበት ሲመሰከር ብሰማም፣ ባለሙያ ለራሱ እውነት ሲል የሚሰብከው ፕሮፓጋንዳ ነበር የሚመስለኝ፡፡
ብሔራዊ ትያትር ቤት ብሔራዊ ሳይሆን አለማቀፋዊ የጥበብ መንፈስን መሸከም የሚችል ህንፃ ነው፡፡ ክፍያው አስራ አምስት ብር መሆኑን ሳይ “ግን” የምትለዋ የቅሬታ ቃል ተመልሳ  ነገሰችብኝ፡፡ ለጥበብ አፍቃሪዎች ጥበብን ከንግድ በማስቀደሙ የትያትር ቤት አስተዳደሩን አመሰገንኩ፡፡ “ግን ትያትር ቤቱ በምን አቅሙ ያድጋል? አዲስ ትያትሮች በምን በጀት ያስተናግዳል? … ግን ቢያንስ የማይረባ ፊልም በሀምሳ ብር ከሚያሳዩ ፊልም ቤቶች ይሻላል፡፡ በአነሰ ገንዘብ የበለጠ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ … “ግን” ስለመስጠቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
ትያትሩ ከመጀመሩ በፊት ሳንድዊች ገዛሁ፡፡ ሳንድዊቹ የፆም ነው፡፡ ትያትር ቤቱ ብሔራዊ ስለሆነ ብሄራዊ የፆም ቀኖች መከበር አለባቸው፡፡ “ግን” መብላት የፈለግሁት የስጋ ሳንድዊች ነበር፡፡ በጥበብ አምልኮ አስራ አምስት ብር መክፈሌ ኪሴን ደስ ቢለውም፣ ለፆም ሳንድዊች አስራ አምስት ብር መጠየቁ አበሸቀኝ፡፡ ሁለቱ በምንም በኩል እኩል አይደሉም፡፡
ባቢሎን በሳሎን › (ይበልጣል) ከሩዝ ሳንድዊች!
“ግን” ከአስራ አምስት ብር ያነሰ ዋጋ ያለው ሳንድዊች የትም ሰፈር የለም’ኮ፡፡ የትያትሩን ሂሳብ ከሳንድዊቹ ማስበለጥ የአስተዳደሩ ፈንታ መሆን ነበረበት፡፡ በሳንድዊች መጠን እንዳይተመን ወይንም አንድ ፊቱን ትያትሩን በነጻ ጋብዞ የጥበብን ነፃነት ማስመስከር ይሻል ነበር፡፡ ጥበብ ከሳንድዊች መብለጡን የብር ተመን ጭራሽ ባለመጠየቅ … ማስረገጥ፡፡ ትያትር ይበልጣል ከሳንድዊች፡፡ ግን መብለጡን የሚያሳየው ያነሰ ብር በመቀበል ነው፡፡ “ግን” ይሄም ወለፈንድ ነው፡፡
ትያትሩን በተመስጦ ተከታተልኩት፡፡ ትያትረኞቹ ከእስክሪፕት በላይ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹን ከዚህ ቀደም በፊልም ወይንም የቴሌቪዥን ድራማ ላይ አይቻቸዋለሁ፡፡ ግን በመድረክ ላይ እንዳላቸው ብቃት አይደለም በእስክሪን ላይ ከዚህ በፊት የተረዳሁዋቸው፡፡ ትያትር ላይ በካሜራ የሚቀረፅም ኤዲት የሚደረግም የለም፡፡ ትክክለኛ ብቃት ነው፡፡ ትክክለኛ ብቃት ባለው ትያትር ቤት ውስጥ ትክክለኛ ብቃት ባላቸው ተዋንያን ሲከወን አየሁ፡፡ ሳንድዊቹን ከግማሽ በላይ መብላት አቅቶኝ በሶፍት ጠቅልዬ የማስቀምጥበት ቦታ አጣሁ፡፡ ትያትሩን “ግን” በሙሉ አጣጣምኩት፡፡ አጣጥሜ ስጨርስ ቆሜ ለአስደነቁኝ ሁሉ አጨበጨብኩ፡፡ እነሱም በጭብጨባ የሚረኩ መሰለኝ፡፡ ግን ጭብጨባ እህል አይሆንም፡፡ ሳንድዊች ትያትር እንደማይሆነው ሁሉ፡፡ ግን በእንደዛ አይነት ፍቅር ገጸ ባህሪዎቹ የሚተውኑት ጭብጨባ ፍቅር ቢሆን ነው፡፡ ፍቅር ደግሞ እርካታ፡፡
ግን እነዚህ አርቲስቶች በደንብ እንዲሰሩ አዲስ ትያትር ተፅፎ በአዲስ ትያትር ቤቶች ውስጥ አይታይም? ለምን በአገሩ ላይ አይስፋፋም፡፡ ትያትር › ከፊልም፡፡ “ግን” ፊልም ብዙ ብር በማስገባት ትያትርን ይበልጠዋል፡፡
ማሳያ ሁለት፡- መሰረተ ልማት
መብራት፣ መንገድ፣ ስልክ፣ መጠለያ አዎ ተስፋፍተዋል፡፡ መስፋፋት መጠናከር ነው፡፡ መጠናከር ከመዳከም ይበልጣል፡፡ ግን እርግጠኛ ነኝ መዳከም ከመጠንከር ስለማነሱ? መብራት እንደ ድሮ በወር እየሄድኩ መብራት ኃይል መክፈል ቀርቷል፡፡ ካርድ እገዛለሁ፤ የመቶ ብር ካርድ ከሶስት ወር በላይ ያስጠቅመኛል፡፡ “ግን” መብራት ብዙ ጊዜ የለም፡፡ ለምን እንደማይኖር ለማጣራት ያደረኩት ሙከራ በሙሉ ወደ መልስ ሳይሆን ወደ መቀየም ነው ያመራኝ፡፡ የመቶ ብር ካርድ ለመሙላት ስሄድ የሚቆረጠው ገንዘብ የተለያየ የሚሆንበት ምክኒያት አልገባኝም፡፡ አንዳንዴ ስድስት ብር፣ ሌላ ጊዜ ሀያ ሰባት ብር ከመቶው ላይ ታክስ ተብሎ ይቆረጣል፡፡ ምክንያቶች ግልፅ ስላልሆኑ ለግልፅ ነገርም ምክኒያት የመጠየቅ አቅሜን አጥቼዋለሁ፡፡
ከመሰረተ ልማት ሁሉ በጣም ያደገው ስልክ ይመስለኛል፡፡ ግን ያለ ስልክ ድሮ የማገኛቸው ሰዎች፣
 አሁን ስልክ እያለ የበለጠ የመራቃቸው ነገር ይገርመኛል፡፡ ሰውን በግንባር ከማግኘት በፌስቡክ ማግኘት መቀራረብ ነው ወይንስ መራራቅ? የሚለው ጥያቄ ራሱ ግልፅ አልሆነልኝም፡፡
መንገድም ተመሳሳይ ነገር አለው፡፡ መንገድ መዘርጋት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የምኖረው ድሮ ስማቸውን ሰምቼ በማላውቃቸው አካባቢዎች ነው፡፡ መንገድ መሰራቱ ጥሩ ነው ግን ከሰፈሬ አርቆኛል፡፡ መንገድ መሰራቱ ጥሩ ነው፤ ግን መንገዱን የሚያክል ፎቅ አብሮት ይገባል፡፡ መንገዱን እና ፎቁን የማናክለው እኛ ጥቃቅኖቹ ከአካባቢው መራቅ ተገድደናል፡፡ ቅርብ የነበርነው ስንርቅ፣ ራቅ ያሉት ደግሞ ቀርበዋል፡፡ አድገናል ግን ተራርቀናል፡፡ ተለውጠናል ግን ተጠፋፍተናል፡፡ በልፅገናል ግን ደስታ የለንም፡፡ ስልክ ሁላችንም አለን ግን ኔትወርክ አይሰራም፡፡ መብራት በአዳዲስ አካባቢዎች ተስፋፍቷል ግን ከነባሮቹ አካባቢዎች እየተቀነሰ ይመስል ፊተኞቹ ኋለኞች ሆነዋል፡፡ እድገት አለ! ግን …፡፡
ማሳያ ሶስት፡- ባንክ፣ ዴሞክራሲ እና ቢራ
ቅድም መፃፍ ስጀምር “ይበልጣል ይበልጣል ነው” ብያለሁ፡፡ ይህ ድምዳሜ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ሊያወዛግበን አይገባም፡፡ ለምሳሌ “ከእኩይ መልካም ይበልጣል” የሚለው ፅንሰ ሀሳብ ላይ ለመጨባበጥ የምናቅማማ ከሆነ ስለ መብለጥ እና ማነስ ደረታችንን ነፍተን መናገር አንችልም፡፡
ወደ መልካም የሚደረስባቸው አማራጮች ግን እየተፎካከርን ለመለየት መጣር ግዴታችን ነው፡፡ ማን ከማን ይበልጣል? ብለን የምንወዳደረው ሁላችንንም ወደሚያስተሳስር ብልጫ ለመድረስ መሆን አለበት፡፡ ወደ ሰው ልጅ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት ወይንም ወደ ደስታ ለማምራት ማን ከማን ይበልጣል ተባብለን ልንሽቀዳደም እንችላለን፡፡ ይህ ማለት ግን ከየትኛው የሰው አይነት የትኛው የበለጠ ነው ማለታችን አለመሆኑን ከፅንሰ ሀሳብ ጀምረን ማጣራት ይጠበቅብናል፡፡
ከህዝብ እና ከመንግስት ማን ይበልጣል?
ህዝብ ነው እንደምትሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ “ግን” … መንግስት ህዝብን ይቆጣጠራል፡፡ ህዝብ መንግስትን ይመርጣል፡፡ ግን መንግስት በህዝብ እኩልነት ስም የበላይ ይሆናል፡፡
ከግለሰብ እና ከማህበረሰብ ማን ይበልጣል?
አይታወቅም፡፡ እንደ ስርዓቱ መልሱ ይለያያል፡፡ እንደ መለያየቱ መጠን የዴሞክራሲ ትርጓሜ ራሱ አንድም ከመስፋቱ የተነሳ ማሟላት የማይቻል ይሆናል፤ አልያም ከመጥበቡ ብዛት ትንፋሽ  የሚያሳጣ ሆኖ ያርፋል፡፡ ከእዝ ኢኮኖሚ ነፃ ገበያ ይበልጣል? ከነፃ ገበያ እና በመንግስት ቁጥጥር ከሚነዳ ገበያስ?
ሁሉም ግልፅ አይደሉም፡፡  
አንድ መአከላዊ ባንከል ካለበት የደርግ ዘመን፣ ወደ ብዙ የግል ባንኮች ዘመን ተሸጋግረናል፡፡ እንደ ባንኮቹ ሁሉ ከሜታ እና ከጊዮርጊስ ወደ አንበር እና ዋልያ ቢራ ዘመንም ደርሰናል፡፡ ባንኮቹ የብሄር መዋቅር ያላቸው ስለመሆናቸው ይወራል፡፡ “እንትና ባንክ የእንትኖች ነው … እንትና ባንክ አክሲዮን ለመግዛት እንትን መሆን ይኖርብሃል” … ወዘተ፡፡
በአጭሩ እንትን ባንክ አገልግሎቱ የበለጠ የሚሆንላቸው ለእነ እንትና ነው እንደማለት ነው፡፡ አገልግሎቱን ሳይሆን የማንነት እምነቱን ግንዛቤ ውስጥ ይዞ ነው አገልጋዩ የሚጠጋው፡፡
ምርጫ = ብሔር
ቢራም ተመሳሳይ ነው፡፡ የአንድ ቢራ አፍቃሪ አንድ እንጂ ሌላ ክለብ አይደግፍም፡፡ ክለቡም ቢራውም የመጠጥ ምርጫውም ከማንነት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ከግለሰብ እና ከማህበረሰብ ማን ይበልጣል? ከተባለ በወቅታዊ ሁኔታ መልሴ “ብሔር” የሚል ይሆናል፡፡
ዲሞክራሲ ወደ ግለሰብ አልወረደም፡፡ ግን ዲሞክራሲ በግለሰቦች ምርጫ እና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አልነበረም ወይ?
ከቅርብ ጓደኛዬ አንዷ ባንክ ያስቀመጠችውን ብር ጠቅላል ልታወጣ ስትል “ግን ሁሉንም ባታወጪው ይሻላል” የሚል ምክር ተሰጣት፡፡ “ግን” የባንክ ሳይንስ ውስጥ እንዲህ አይነት ጣልቃ ገብነት ይፈቀዳል እንዴ? በሌላ ጊዜ እቺው ልጅ ከተረፋት ሶስት መቶ ብር ሁለት መቶውን ልታወጣ ስትል፣ የባንኩ ሰራተኞች እንደሳቁባት ነገረችኝ፡፡ እንግዲህ ባንኩን የመሰረተው ብሔር ገንዘብን በማጠራቀም እንጂ ባለመቀነስ የሚያምን ሊሆን ይችላል፡፡ … ግን ለግለሰቧ ደንበኛ ይህ እምነት ምን ያገባታል? በፈለገችው ጊዜ ገንዘቧን ማስቀመጥ፣ በፈለገችው ጊዜ ማውጣት የምትችለው፣ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልደው ባደጉ ልጆች የተመሰረተ ባንክ ስራ የጀመረ ዕለት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ግን ይኼ ሁሉ ነገር ከባንክ ሳይንስ ጋር ምን አገናኘው? የባንክ ሳይንስ ከብሄር ሳይንስ ጋር ከተደባለቀ አዳዲስ አባዜዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡
የብሔር ዴሞክራሲን ከግለሰብ ነፃነት ጋር ለማነፃፀር፣ ቢራ እና ባንክን እንደ ምሳሌ ማየቴ ስህተት አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም ከዛም በላይ ገፋ ማድረግ ይቻላል - የቁርኝት ሰንሰለቱን፡፡ እንትና የተወለደው የት ነው? ያደገውስ … የሚለው ጥያቄ መልስ ካገኘ … የሚጠጣውን ቢራ፣ የሚቆጥብበትን ባንክ፣ የሚገዛውን ጋዜጣ … እና የሚያደምጠውን ሀገርኛ ዘፈን ማወቅ ይቻላል፡፡
ማን ከማን ይበልጣል?! የሚለው መንፈስ ሁሉም የሰው ልጅ  በተለይ ደግሞ የሀገር ልጅ አንድ እንደሆነ በታመነበት ሁኔታ መልካም ፉክክር ነው፡፡ ማን ከማን ይበልጣል ብሔርን ወይንም በተለያየ የመድሎ እርከን ላይ ተቀምጧል ተብሎ የሚታሰብን ማህበረሰብ መሰረተ ያደረገ ከሆነ … “ግን” ጥርጣሬ ሳትጠራ “አቤት” ትላለች፡፡
“ሀገር እያደገ ነው፣ ሰው በተሻለ ነፃነት እየሰራ ነው፣ ብዙ አማራጮች ተፈጥረዋል”
… “ግን”
ማሳያ አራት፡- እንጀራ
ስም መደብለቅ (Name dropping) አይሁንብኝና በቅርቡ አዳም ረታ ስምንተኛውን መፅሐፉን ለማስመረቅ አዲስ አበባ በነበረበት ወቅት ከእሱ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የመገናኘት እድል አግኝቼ ነበር፡፡
እና ምን ይጠበስ? ካላችሁኝ …. ጥብስ ሳይሆን በሥነ-ፅሁፉ ላይ አዘውትሮ የሚጠቅሰውን እንጀራ ፍርፍር በፍላጎት አዝዞ “ግን” መመገብ አቅቶት ሲተወው ታዝቤ ነበር፡፡ እንጀራን “ሜታፎር” አድርጎ ድርሰቱን በእንጀራው ፍልስፍናው ውስጥ እየፈጠረ ያለው ደራሲ፤ እንጀራ ቀርቦለት ሳይበላ “በቃኝ” ሲል ትንሽ ብገረምም ችግሩ ያለው የት እንደሆነ ወዲያው ሳይገባኝ አልቀረም፡፡
ቢገባኝም ለእሱ “ግን” አልጠቀስኩበትም፡፡ አዳም ስለ እንጀራ የማይለወጥ ታሪክ እና ቅርፅ ሲጨነቅ፣ እንጀራ መበላሸቱን ልብ አላለም፡፡ እንጀራ ተበላሽቷል፡፡ መበላሸቱን በይፋ ያወጀው የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ነው፡፡
በፊት፤ ችግሩ፤ የጤፍ ዋጋ ጣራ መንካቱ ጤፍን ከተለያዩ ንጥረ ነገሮች ጋር እየቀላቀሉ ስለሚጋግሩት ይመስለኝ ነበር፡፡ ጤፍን ከሩዝ … ከበቆሎ ወዘተ፡፡ ነገሩ “ግን” እንደዛ አይደለም፡፡ እረፍት ያጡ የእርሻ መሬቶች ላይ ያለ አፈር ሚኒራሉ ስለተሟጠጠም አይደለም፡፡ ወይንም በእርሻ መሬቶች ላይ የሚፈሰውም ማዳበሪያ አይመስለኝም… ለእንጀራው መበላሸት አስተዋፅኦ ያደረጉት፡፡
የእንጀራውን መበላሸት እኔ የማውቀው ወደ ውስጥ ሲገባ በሚፈጠረው ስሜት ነው፡፡ ተበልቶ ወዲያው ከሆድ ይጠፋል፡፡ ወይንም በጭራሽ     አይፈጭም፡፡ በተለይ ከሽያጭ የምገዛቸው እንጀራዎች ከጣዕማቸውም፣ ከሽታቸውም ብዙ እንከን ስላለባቸው አግልያቸዋለሁ፡፡ ምናልባት አዳም ላይም ይህንኑ ነገር ሳይሆን አይቀርም የታዘብኩት፡፡
“ግን” እንጀራ ይኼንን ያህል የአበሻ ማንነት አርማ ከሆነ፣ እንጀራው እየወደቀ አበሻ ቢነሳ… አነሳሱ ጥርጣሬ ያዘለ አይሆንም? … ድሮ እንጀራ ተበላሸ ማለት ሻገተ ነው፡፡ አዲሱ አበለሻሸት አዲስ ትርጓሜ ያስፈልገዋል፡፡… ግን እንጀራ ከተበላሸ ምን እንብላ? … ኢንዶሚን?!
አምስተኛ ማሳያ፡- ሴቶች
ልዩነቶችን እኩል ማድረግ እንጂ አንድ ማድረግ አይቻልም፡፡ ሴቶችን እኩል ለማድረግ የተሰሩት ስራዎች ጥሩ ናቸው፡፡ ግን ሴቶችን ሀያል ማድረግ ማለት ሁሉንም ሴት ማድረግ ስለአለመሆኑ መጣራት ይገባዋል፡፡ ልክ መንግስን የህዝብ ምርጫ ለማድረግ ህዝብን በመንግስት ካድሬዎች እና አፈቀላጤዎች መሙላት እንደመሰለው እንዳይሆን ማለቴ ነው፡፡
ልዩነቶች በእኩል ሁኔታ ቦታ መቀያየራቸው (ማለትም እናት የመሰሉ አባቶች እና አባት የመሰሉ እናቶች) መፈጠራቸው ለልጆቻቸው የተሻለ ወላጅነትን የሚፈጥር መሆኑ ታምኖበት ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ “ግን” የታመነበት በማን ነው? … እናቶቻችን ስኬታማ ሴት እንዳልነበሩ በራሳቸው አንደበት ከሚናገሩት ይልቅ የእነሱ ባልሆነ እምነት የሚናገሩላቸው ተደማጭነት አግኝተዋል፡፡
ተፈጥሮ ይበልጣል ወይንስ ተሞክሮ? …
ተፈጥሮን የሚለውጡ ተሞክሮ እንዲጸድቅ የተደረገው ለሴቶች የተሻለ እድል እንዲሰጥ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ “ግን” ተሞክሮውን ፖሊሲ ያደረጉት ሰዎች ሴቶች እንዳይደሉ ይሰመርበት፡፡ “አንኳሩ የስልጣን ስፍራ ላይ የተቀመጡት አሁንም ወንዶች ናቸው፡፡ ሊቃነ ስልጣናቱ ለሚስቶቻቸው አሁንም የበላይ ናቸው፡፡ ለሚመሩት ህዝብ ያስተካከሉት ተሞክሮ በእነሱ ዘንድ መስራቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ የተስፋዬ ገ/አብ መፅሀፍ ስለነዚሁ ቁንጮዎች የሚለው ነገር እውነት ይሁን ሀሰት የሚያውቁ ይመዝኑት!
የተፈጥሮ ህግን ለማስተካከል መስራቱ … የወንድ ትምክህተኝነትን በሴት እኩልነት ለማስተካከል መጣሩ ተገቢ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ “ግን” እኩልነቱ ከላይ ነው መጀመር ያለበት፡፡ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሚስቶቻቸውን ከጓዳ አውጥተው ስፍራውን ይልቀቁላቸው፤ ከዛ ከእነሱ አርአያነት የተማረ ህዝብ በተግባር ይከተላቸዋል፡፡ ግን እውነት ተፈጥሮን ተሞክሮ ይቀይረዋል? … “ተፈጥሮን ተሞክሮ ወይ ያጣምመዋል ካልሆነ ያሳምፀዋል” ብለው ነው ያስተማሩን፡፡

Published in ህብረተሰብ


የስልጤ ዞንዋ ወራቤ ከተማ እንደ አገሩ በሠርጓ ዋዜማ ኮሶ ጠጥታ፣ ለሠርጓ የተዘጋጀች ኮረዳ መስላ ታየችኝ፡፡ ከአራትና አምስት ዓመት በፊት ያየኋት ጨቅላዋ ወራቤ አይደለችም፡፡ ዛሬ ጡቶችዋን ደረትዋ  ላይ ቀስራ፣ባል በውበት ፉጨት፣ በነፍስ ዜማ የምትጠራ ትመስላለች፡፡ ደምዋ መፍለቅለቅ፣ አይኖችዋ መናጠቅ እየጀመሩ ነው፡፡ ገና አሥር ዓመቷን በቅርብ ያለፈችው ወራቤ ስሟ ከየት መጣ? ከብዙ ሰዎች ድምር ሃሳብ ተጨምቆ የተገኘው የስልጤ ታሪክ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡- ወራቤ ቀድሞ “ወርኮ” ነበር አንድ ስሟ፡፡ ወርኮ ደግሞ የገበያ ስም ነው፡፡ ገበያ ደግሞ የእንጀራ ምጣድ እንደ ማለት ነው - በኔ ትርጓሜ፡፡ እና በእንጀራ ወይም በዳቦ ስም ጠሯት፡፡ ለነገሩ ሕይወት ሁሉ በእንጀራ ምጣድ ለእንጀራ ተሽከርክራ አይደል ጣዕምዋን መጥጣ፣ ሥጋዋን ቆርጣ ስታበቃ፣ ከምህዋሩ የምትወረወረው!
እናም “ወርኮ” ያኔ ጥንት በደቡብ እስከ ከፋ፣ ከደቡብ ምዕራብ እስከ መተማ ለሚያልፉ የሲራራ ነጋዴዎች መተላለፊያ ነበረች፡፡ በጊዜው ጥጥ፣ ቡናና ዝንጅብል ታመርት ነበር፡፡ ቅመሞችዋም የብዙዎችን ልብ ነጥቀዋል፡፡ ያ ብቻ አይደለም፡፡ የባሪያ ንግድም የጦፈባት ገበያ ነበረች፡፡
“ወርኮ” የሚለው የስልጤኛ ቃል ጥሬ ትርጉሙ “ዞር በል!” ወይም መክቶ መላሽ እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ ትርጉም የተሰጠው ደግሞ በሥፍራው የነበረውን ጦርነትና የጦርነቱን ጀግኖች በማሰብ ነው፡፡ ለወቅቱ ድል ደግሞ ስንኞች ተቋጥረው፣ በዜማ ተንቆርቁረዋል ይባላል፡፡ ልጃገረድዋ የእህል ወፍጮ ላይ መጇን ወደፊትና ወደኋላ እየገፋች፣ ጐረምሳው በዜማና በፉጨት በአየር ላይ አናኝቶታል፡፡
በስልጢኛ - “በሶመን ስላት
በመህሪባ ገባት
ኡሀም ባፍጥር ሳት
ለኩተሬ ታት
መጣን በለፋት
ሚን ቢቾ ደረሰ፣ ሚሽቱም ቲጃጄት”
በአማርኛው - “በፆም በሶላት፣
        በመግሪብ ሶላት ወቅት
ከኩተሬ በላይ፣ ጀግና መጥቷል አሉ
የቁርዐን ተማሪ (ደረሳ) ብቻ ሳይሆን ሴቷም ተዋግታለች፡፡
(ትርጉም - ከመጽሐፉ ደራሲ ከይረዲን ተዘራ)
ሌላኛው ትርጓሜ - በስልጢኛ ቋንቋ “ወራባ” ማለት ጅብ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ ጦረኞች ወደ ሌላ አካባቢ ወረራ ሲያደርጉ ጅብ ናቸው እንዴ? ለማለት “ወራባ” ሲሉ፣ በጊዜ ሂደት ያ - የጦር አውድማ፣ ያ - የጦረኞች ድንኳን “ወራቤ” ተብሎ ስያሜዋን ቀየረው ይላል - የስልጤ ታሪክ ፀሐፊ የከይረዲን ተዘራ መረጃ፡፡ ሌላው ደግሞ “ወረብ” ከሚል ቃል የመጣ ነው ይላል፡፡
የአሁንዋ ወራቤ አቀማመጧ ለተፋሰስ አመቺ ነው፤ ለአይንም የሚማርክ መልክዓ ምድር አላት፡፡ በተለይ ኮምፕሬሲቫል ሪፈራል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሏ ታላቅ ግርማ አጐናፅፏታል፡፡ የዞኑ የባህል ማዕከልም በሳር ቤት ቅርፅ፣ አሣምረው ስለሰሯት በእጅጉ ታባብላለች፡፡ ነፍስ ትማርካለች፡፡ ቀለም ቅብዋም የባህል ልብሱ ላይ መሠረት ያደረገ ስለሆነ፣ ደግና ተገቢ ትርጓሜ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ያንን ቀለም በሆቴሉም፣ በካፌውም በሱቁም ላይ ማድረግ ግን አንዳች የውበት መፋዘዝና መንዛዛት ያመጣል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡
ወራቤ ሲጋጌጡ ይመላለጡ አይነት ለዛ ቢስነት ውስጥ እንዳትገባ ከወዲሁ ለውበቷ መጠንቀቅ የሚያሻት ይመስለኛል፡፡ አገር ምድሩን ተመሳሳይ ማድረግ ሌላው ቢቀር ቦታን ለማወቅ ያደናግራል፡፡ በዚያ ላይ ለዓይንም መሰልቸቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው ባይ ነኝ፡፡ በተረፈ ብቅ ብቅ ያሉት አዳዲስ ህንጻዎች የወራቤ ጌጦች መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በርካታ ገልባጭ መኪናዎች ወደ ወራቤ እንደሚተሙ አስተውያለሁ - አሸዋ ለመጫን፡፡ አሸዋ የተፈጥሮ ሃብቷ ነው፡፡ ለሆነለት እኮ አሸዋም ወርቅ ነው፡፡  
የወራቤና የስልጤ ልማት ጥሩ መልክ ነው ብዬ የምጠቅሰው፣ ከየወረዳው የተውጣጡ ጐበዝ ተማሪዎችን ማደሪያ ቤትና ምግብ በማዘጋጀት ለማስተማር መትጋቷን ነው፡፡ ይህ ለነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ነው፡፡ አቅም በማጣት እንደ እሣት የሚነድዱ፣ እንደ መብረቅ ጨለማን የሚሰነጥቁ ወጣቶች፣ በእንጀራ ታንቀው እንዳይቀሩ መታደግ ያኮራል፡፡
በሠሞኑ የወራቤ ጉዞዬ ዋነኛው ትኩረቴ የነበረው አንድ የስልጤ ጐልማሳ ነው፡፡ ከድር አብዱ ይባላል፡፡  ትንሽ የሚያደናግር ሕይወት፣ የሚጐፈንን ትዝታ አለው፡፡ ወጣትነቱን በቀለም ቤንዚን ነድዷል፣ ጐልማሣነቱም አመድ አልዋጠውም፤ ዛሬም የጥበብ ፍም ነው፡፡ ጠጋ ላለው ይሞቃል፣ ላዳመጠው ደማቅ የነፍስ ዜማ ነው፡፡ ከድር አብዱ ከረጅም ዓመታት በፊት የጂማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተማሪ ነበር፡፡ ሦስተኛ ዓመት ላይ አንድ መምህር “እግርህ ያነክሣልና መማር አትችልም” ብሎ እንዳባረረው ይናገራል፡፡  ከድር በውጤቱ አይታማም፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባው ከአንድ “B” በስተቀር “A” ዎችን ደርድሮ ነው፡፡
ግን ምን ያደርጋል-- በአንድ መምህር የተነሳ ትምህርቱን አቋረጠ፡፡ ወደ ቀዬው ተመልሶ እርሻ ጀመረ፤ ጥሩ ገበሬ ወጣው፡፡ በተለይ ደግሞ በርበሬ ያመርት ነበር፡፡ ግን ብስጭቱ ሲቀሰቀስ መለኪያን ባልንጀራው ያደርጋል፡፡ የሕይወት ፉንጋ ፊት ሲያስጠላው፣ መለኪያ ውስጥ ውበት ያስሳል፡፡  
ከድር ላለፉት 20 ዓመታት ከትምህርት ጋ ከእነአካቴው አልተለያየም፡፡ ተማሪዎችን ያስጠናል፣ ያስተምራል፡፡ እሱ ያስተማረው ተማሪ ደግሞ ውጤቱ የታወቀ ነው፡፡ ስለ ዕውቀቱ ሀገር ይመሠክርለታል፡፡ ከድርን ከዚህ ቀደም አግኝቼው አውግቶኝ ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ከረጅም ዓመታት በኋላ ዳግም አወጋን፡፡ አሁን ከ1ኛ-8ኛ ክፍል የስልጢኛ ቋንቋ ማስተማሪያ መርጃ፣ ከ9-10ኛ ክፍል ማስተማሪያ መርጃ፣ በተጨማሪም ከ5-12ኛ ክፍል የስልጢኛ ቋንቋ ማስተማሪያዎች አጋዥ መጻህፍት አዘጋጅቶ አውጥቷል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከ150 በላይ ገፆች ያሉት ልቦለድ መጽሐፍ በስልጢኛ ቋንቋ ጽፏል፤ የግጥም ጥራዞችም አሉት፡፡ ግን አሁንም ትራሱ ሥር ሀሳብ እየበላቸው፣ የእርሱንም ሃሳብ እየበሉ ቀርተዋል፡፡
ከድር መፃፍ ብቻ አይደለም የሚወድደው፣ ማንበብ ሕይወቱ ነው፡፡ የስልጢኛ ቋንቋ አጋዥ ማስተማሪያዎችን ለመፃፍ በርካታ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋ መፃሕፍትን አንብቧል፡፡ ስለ ግጥም ሲፅፍ ዘይቤዎችን፣ ቋንቋ አጠቃቀምን፣ ምትንና ምጣኔን በወጉ አውቆ ነው፡፡
ከፃፋቸው ግጥሞች ውስጥ ጥቂት ስንኞችን ወስጄ በወዳጄ መሐመድ ሁሴን ትርጉም ላስነብባችሁ፡ -
ታወሠኝ ፍስኩ ቀን ደምቆ የማለዳው፤
የቄጠማ ምንጣፍ ለብሶ
ሽታው ሲናኝ እልፍኝ ጓዳው
ክትፎ ዓይቡ በየአይነቱ፣
ፌሽታ ሲሆን ተሰብስቦ ጐረቤቱ፣
ከእናት ጋራ መደሰቱ!
ብዙ ግጥሞቹ የፍቅር፣ የማህበራዊ ሕይወት፣ የባህል - ጣዕም ያጠቀሱ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ  ተማሪዎችን ሲያስጠና የትምህርት ዓይነት መርጦ አይደለም፤ ሁሉንም ነው የሚያስተምረው፡፡ ፊዚክስ፣ ሂሣብ፣ እንግሊዝኛ፣ አማርኛ… ሁሉንም ያስጠናል፡፡
ከድር ባለፈ ነገር መፀፀት የሚወድ ሰው አይደለም፡፡ በትምህርቱ ያሰበበት ድረስ ባይገፋም ሌሎች ልጆች ላይ በሚዘራው ዘር ደስ ይሰኛል፡፡ ብዙ ታላላቅ ሰዎች ፈጥሬያለሁ ይላል፡፡ የሚገርመው ግን በዚህ ዘመን አንድ ገጣሚና ደራሲ ብቅ ያለለት የስልጤ ሕዝብ፣ የዚህን አንድ ዕንቁ ድምጽ መስማት ያለመቻሉ ነው፡፡ ለሰዎች ጤንነት፣ ማሕበራዊ ደህንነት ያንን ታላቅ ሆስፒታል ያሠራ ሕዝብ፣ እንዴት አንድ የጥበብ ሻማ የሆነውን ጌጡን የመከራ ንፋስ እያጣፋ ብርሃኑን ሊነጥቅ ሲታገል ዝም ይላል? ይህ ነው ግራ አጋቢና አያዎ (paradox) የሚሆነው፡፡ ይህን ምጡቅ ምናብና አእምሮ የታደለን ወጣት፤ ዞኑ በርቀት ትምህርት እንኳ የተሻለ ሥልጠና እንዲያገኝ ሊረዳው እንዴት አልቻለም? ከዚያ ባለፈ የአካባቢው ተወላጆች ይህችን ቀላል ጥያቄ እንዴት መመለስ አቃታቸው? እንደ እኔ እንደ እኔ ግን ከድር አብዲ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለታላቅ ሀገራዊ ጥቅም የሚውል አቅም ያለው ብርቱ ሰው ነው፡፡ በሕይወት እያለ ሊጠቀሙበት የሚገባ ስለሆነም የእርሱ ጉዳይ ሁላችንንም ይመለከታል ባይ ነኝ፡፡ ይህንን ንፋስ የሚያወላግደውን ብርሃን፣ መስታወት ሆነን ከመጥፋት እንታደገው፡፡  

Published in ህብረተሰብ
Monday, 02 March 2015 09:30

የጀግንነት ጥግ

ድልን ጠብቅ፤ ድልም ታደርጋለህ፡፡
ፕሪስተን ብራድሊ
(አሜሪካዊ ቄስ)
አሸንፋለሁ ብለህ ካሰብክ ታሸንፋለህ፡፡ ድል ለማድረግ እምነት ወሳኝ ነው፡፡
ዊሊያም ሃዝሊት
(እንግሊዛዊ ወግ ፀሐፊና ሃያሲ)
በምርጫው ለተሸነፉት ሁሉ አዝናለሁ፡፡ ይሄ እኔ የማውቀው ተመክሮ አይደለም፡፡
ማርጋሬት ታቸር
(የቀድሞ የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር)
 ድል ሺ አባቶች አሉት፤ ሽንፈት ግን ወላጅ አልባ ምስኪን ነው፡፡
ጆን ፊትዝገራልድ ኬኔዲ
(የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)
የሰው ልጅ ትልቁ ድል ራሱን ድል ማድረግ ነው፡፡
ጆሃን ሔይንሪክ ፔስታሎዚ
ተመልከቱ፤ ድል አድራጊው ጀግና መጣ!
       ጡሩንባው ይነፋ፤ ከበሮው ይመታ!
ቶማስ ሞሬል
(እንግሊዛዊ የመደብ ልዩነት አቀንቃኝ)
መደበኛ ጦር ካላሸነፈ ይሸነፋል፡፡ ሽምቅ ተዋጊ ካልተሸነፈ ያሸንፋል፡፡
ሔነሪ ኪሲንጀር
(አሜሪካዊ ፖለቲከኛና ዲፕሎማት)
ሽንፈትን መቀበል የሚችል አንጀት ካለህ አታሸንፍም፡፡
ቪንስ ሎምባርዲ
(አሜሪካዊ የእግር ኳስ አሰልጣኝ)
አስቤው የሆነ አይደለም፡፡ ጀልባዬን አስጠሙብኝ፡፡
ጆን ፊትዝገራልድ ኬኒዲ
(እንዴት ጀግና ሊሆን እንደበቃ ሲጠየቅ የመለሰው)
ዓለም በደስታ ብቻ የተሞላች ብትሆን ኖሮ ጀግንነትንና ትዕግስተኛነትን አንማርም ነበር፡፡
ሔለን ከለር
(አሜሪካዊ ፀሐፊና መምህር)
ድፍረት የተስፋ ፍሬ ነው፡፡
የፊሊፒኖች አባባል
ለሰው ልጅ አንዳች ድል እስክታመጣ ድረስ ሞትን ተጠየፍ፡፡
ሆራስ ማን
(አሜሪካዊ የትምህርት ባለሙያ)

Published in ጥበብ

“ዶ/ር ተክለፅዮን ጠንካራ መሪ ባይሆኑ ኖሮ ምናልባትም ዛሬ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚታወቅበትና የሚኮራበት የጤና ሳይንስ ላይኖር ይችል ነበር” - ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ - የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት


   ዶ/ር ተክለፅዮን ወ/ማርያም በሙያቸው ለግማሽ ምዕት ዓመት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መኖሪያቸውን በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት የቀድሞ ተማሪዎቻቸው ዶ/ር ተክለፅዮን፣ የህክምና መምህር፣ መጽሐፍት፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ላቦራቶሪ፣ … ምንም በሌለበት አስተምረውና እውቀት አስጨብጠው ለዛሬው ማንነታቸው እንዴት እንዳበቋቸው ምንጊዜም አይዘነጉትም፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት እነዚያ ዶክተሮች የሚወዷቸውንና የሚያከብሯቸውን የቀለም አባታቸውን ወደ አሜሪካ ጠርተው ማመስገን ፈለጉ፡፡ በዚህ መሰረት ለክብራቸው በዋሽንግተን ዲሲ እራት አዘጋጅተው ጋበዟቸው፡፡ በሥነ-ስርዓቱ ላይ በተማሪነት ዘመናቸው ያጎናፀፏቸውን እውቀት መክፈል እንደማይችሉት ቢያውቁም ጥቂት ነገር በማድረግ ሊያመሰግናቸው እንደሚፈልጉ ገለጹላቸው፡፡
ዶ/ር ተክለፅዮን ግን የምታደርጉልኝን ነገር ሁሉ ከጅማ ጤና ሳይንስ ጋር የተያያዘ ይሁን አሉ፡፡ “ሐሳባችንን ወደ አዲስ አቅጣጫ አዞሩት” ይላል የሀሳቡ ጠንሳሽና የቀድሞ ተማሪያቸው ዶ/ር ዳውድ ሲራጅ፡፡ ምን እንደሚያደርጉላቸው ሲወያዩ “ለምን በጅማ ዩኒቨርሲቲ በስማቸው ፋውንዴሽን አናቋቁምላቸውም?” የሚል ሐሳብ ቀረበና ሁሉም በአንድ ድምፅ ተስማሙ፡፡ “በዚያን ምሽት በተደረገው ውይይት ከ80 ሺህ ዶላር በላይ ቃል ተገባ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እኔ በበጎ  ፈቃደኝነት በብዙ ድርጅት እሳተፋለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ቃል ከተገባው ውስጥ ግማሽ ያህሉ እንኳ አይሰበሰብም፡፡ ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው በዚያን ዕለት ስብሰባ ቃል ከተገባው ውስጥ 100 ፐርሰንት ተሰበሰበ፡፡ በ2ኛው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ60 በመቶ በላይ ገንዘብ ተገኘ፡፡ ዋና መስራቾች ተሰብሰብን በፋውንዴሽኑ ዘላቂነትና ቀጣይነት ላይ ተወያይተን ነበር፡፡ በቀጣይነቱ ላይ ሁላችንም በአንድ ቃል ተስማማን” ብሏል ዶ/ር ዳውድ፡፡
የፋውንዴሽኑ ምስረታ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተከናወነው ባለፈው ታህሳስ ወር ቢሆንም በህመም ምክንያት ዶ/ር ተክለፅዮን በሥነ ስርዓቱ ላይ አልገተኙም ነበር፡፡ ስለዚህ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ዶክተሩ አሁን ወደሚኖሩበት አዳማ ሄደው ደስታቸውን አብረው ለማክበር በወሰኑት መሰረት የዛሬ ሳምንት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት አቶ ኮራ ቱሹንና ሌሎችም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በአዳማ ከተማ ተገኝተው ዶ/ር ተክለፅዮንን “እንኳን ደስ አለዎት” በማለት አክብሮትና ደስታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
የሐሳቡ ጠንሳሽ እኔ ብሆንም ስራው ከባድ ስለነበር ሌሎችም ረድተውኛል ያለው ዶ/ር ዳውድ፤ አትላንታ ኗሪ የሆነው ዶ/ር መስፍን ፍራንሷ፣ ከኒውዮርክ ዶ/ር ፋሲል ደስታ፣ ከኖርዝ ዳካታ ዶ/ር ኦልማ ቡሸን፣ ከኒውዮርክ ዶ/ር መስከረም አስረሳኸኝ፣ በኢትዮጵያ ተወካይ እንዲኖረን ዕቅድ ስለነበረን ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀና ዶ/ር ሚካኤል ደጀኔ እዚህ ሆነው ከፍተኛ ድጋፍ ስላደረጉልኝ አመስግኛቸዋለሁ፣ ዕቅዳችን እንዲሳካ ስላደረጉ እናንተም አመስግኑልኝ ብሏል፡፡
ዶ/ር ተክለፅዮን፣ ዕድገት ማለት የህብረተሰቡን ችግር መፍታትና ኑሮውን መቀየር ነው የሚል እምነት ስላላቸው፣ ከ1ኛ ዓመት ጀምሮ ወደ ገጠር እየወሰዱን የአርሶ አደሩን ጓዳና የተጫነውን የድህነት መጠን እንድናይ ስላደረጉን የአርሶ አደሩ ኑሮና ህይወት በውስጣችን ተቀርፆ እንዲቀር አድርገዋል ያለው ዶ/ር ዳውድ፤ ከእሳቸው በኋላ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና አመራር የነበሩት እንዲሁም አሁን ዩኒቨርሲቲውን በመምራት ላይ ያላችሁት ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ አቶ ኮራ ቱሹንና ሌሎችም የዶ/ር ተክለፅዮንን ሐሳብ ደግፋችሁ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ ጤና ትምህርት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቀዳሚ፣ ከአፍሪካ ተመራጭና በዓለም ታዋቂ እንዲሆን እየሰራችሁ ስለሆነ በጣም አመሰግናችኋለሁ፡፡ ዶ/ር ተክለፅዮን፣ ዩኒቨርሲቲውን ለማጠናከር እናንተ በውጭ አገር ያላችሁት ልጆቼ እየመጣችሁ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ግንኙነት ፍጠሩ ስላሉን በዚህ ጉዳይ ላይ እየተነጋገርን ሲሆን በቅርቡ የመጀመሪያውን ፍሬአችንን ለማሳየት ኢንተርቬንሽናል ካርዲዎሎጂ ትምህርት ለማስጀመር መሰረት እየተጣለ ነው በማለት ዩኒቨርሲቲውን ለመደገፍ እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ አስረድቷል፡፡
በውጭ የሚኖሩት የቀድሞ ተማሪዎች፣ የዶ/ር ተክለፅዮን ፋውንዴሽንን ለመመስረት ያቀረቡት ፕሮፖዛል ይህን ይመስላል፡፡ 1ኛ፣ ዓመታዊ የዶ/ር ተክለፅዮን ሌክቸር፡- በአገር አቀፍ ደረጃ በተለይ ለጅማ አካባቢ ማህበረሰብ ጠቃሚና ችግር ፈቺ በሆኑ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ የሚያቀርቡ ታዋቂ ተመራማሪዎችን ስፖንሰር ያደርጋል፡፡ 2ኛ- የዶ/ር ተክለፅዮን ሽልማት፡- ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ዕድገትና ተልዕኮ መሳካት በጥናት፣ በማስተማር ወይም በማኅበረሰብ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ግለሰብ ይሸልማል፡፡
3ኛ - የዶ/ር ተክለፅዮን ነፃ የትምህርት ዕድልና ሜንቶርሺፖ፡- በዚህ ፕሮግራም ከፍተኛ ውጤት (ወደፊት ይገለጻል) እያላቸው በገንዘብ ችግር ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይደገፋሉ፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የዶ/ር ተክለፅዮንን ሌጋሲ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚችል ህንፃ በስማቸው እንዲሰየም አመራሩን እንጠይቃለን የሚል መልዕክት የያዙ ሦስት ፕሮፖዛሎች ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ላኩ፡፡ ዩኒቨርሲቲውም መልዕክቱን የተቀበለው በደስታ ሲሆን የማያቋርጥ ድጋፍም እንደሚያደርግላቸው ገልጾ “የዶ/ር ተክለፅዮን ወ/ማርያም ፋውንዴሽን” ተቋቋመ፡፡
በአዳማው ሥነ - ሥርዓት ላይ ፋውንዴሽን ማቋቋም ቀላል ነገር አይደለም ያሉት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ለዶ/ር ተክለፅዮን ፋውንዴሽን እንዲቋቋም ሲጠየቅ፣ ለራሳቸው ሳይሆን የሕዝብና የአገርን ጥቅም ለሚያስቀድሙ ሰው የዩኒቨርሲቲው ሴኔት የተስማማው በሙሉ ድምፅ ነው ብለዋል፡፡
ጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩትና ጅማ አግሪካልቸራል ኮሌጅን አንድ ላይ አድርጐ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተው በ1991 ዓ.ም እንደነበር ዶ/ር ፍቅሬ ጠቅሰው፣ የግብርናውን ባለሙያ ክህሎት ለማጠናከር በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግሥት በ1944 የተመሠረተውን ኮሌጅ ለሦስት ጊዜ በዳይሬክተርነት የመሩት አሜሪካኖች እንደነበሩና በ1975 ዓ.ም የተመሠረተውን ጅማ ጤና ኢንስቲትዩት ግን በዳይሬክተርነት የመሩት ዶ/ር ተክለፅዮን ወ/ማርያም መሆናቸውን በኩራት ገልፀዋል፡፡
ምንም የተሟላ ነገር (መምህራን፣ መጻሕፍት፣ ቁሳቁስ…) በሌለበት በቆራጥነት አገሪቷን ለማሳደግ የድርሻዬን መወጣት አለብኝ ብሎ ጥቂት ሰዎችን ይዞ የሳይንስ ባለሙያዎችን ለማፍራት መነሳት ከችግርም በላይ ፈታኝ እንደሆነ መገመት አያቅትም ያሉት ዶ/ር ፍቅሬ፣ ዶ/ር ተክለፅዮን ጠንካራ መሪ ባይሆኑ ኖሮ ምናልባትም የጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ዛሬ ጅማ ጤና ሳይንስ የምንለው ክፍል ላይኖረው ወይም በዚያው ሊቀር ይችል ነበር፡፡ እሳቸው ግን እንደመምህር አስተማሪ፣ እንደመሪ ተቋም መርተው፣ በሙያቸው አክመው ዛሬ ዩኒቨርሲቲው ለሚመካበትና ለሚኮራበት የማኅበረሰብ አጋር ለሆነው የጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት መሠረት ናቸው፡፡ ዶ/ር ተክለፅዮን ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሰሶ ስለሆኑ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ታሪካቸውን ምንጊዜም በአድናቆት ያስታውሳል፡፡ ለዚህም ነው ፋውንዴሽኑ እንዲቋቋም የፈቀደው በማለት አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ተክለፅዮን አለቃዬ ነበሩ ያሉት የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት አቶ ኮራ፣ ከእሳቸው ከተማሯቸው ነገሮች ዋነኞቹ ትዕግሥትና ቅንነት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በ1983 መንግሥት ሲለወጥ ጅማ ከተማ በዘራፊዎች ተውጣ ድርጅቶች፣ መ/ቤቶች ሲዘረፉ የከተማዋ ነዋሪ እየሸሸ ሲሄድ ዶ/ር ተክለፅዮን ግን ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ መጥተው ለጤና ሳይንሱ ኢንስቲትዩት የጥበቃ ሰራተኞች ከኪሳቸው ደሞዝ እየከፈሉ ያበረታቷቸው ነበር ብለዋል፡፡
ዶ/ር ተክለፅዮን 31 ዓመት ወዳገለገሉበት ጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የሄዱት በ1975 ዓ.ም ነበር፡፡ ሲሠሩበት ከነበረው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለቅቀው ኮሙኒቲ ቤዝድ ኤጁኬሽን በተባለ አዲስ ፍልስፍና የጤና ባለሙያ እንዲያፈሩ ወደ ጅማ የተላኩት በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል ግዛው ፀሐይ ፊርማ ነበር፡፡  

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁማ!
ይቺን የሆነ ቦታ ያነበብኳትን አሪፍ ነገር ስሙኝማ…አውሮፕላን ውስጥ ነው፡፡ አንደኛው; ሰውየው የምንም አይነት ኃይማኖት ተከታይ አይደለም፡፡ ከጎኑ ያለው ሰውዬ ግን የኃይማኖት መጽሐፍ እያነበበ ነበር፡፡ ኃይማኖት የለሹ ሰውዬም…ተንጠራርቶ አየውና ምን ይለዋል…“እሱ ላይ ያሉ ታሪኮችን ሁሉ ታምናለህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡  
ያነብ የነበረው ሰውዬም… “አዎን፣ አምናለሁ፣” አለ፡፡
ያኛውም ቀጠለና… “እሺ፣ ዮናስ እንዴት ነው በአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀን በህይወት ሊቆይ የቻለው?” ሲል ይሞግተዋል፡፡
ሰውየውም… “እኔ አላውቅም፣ ግን መንግሥተ ሰማያት ስገባ ዮናስን እጠይቀዋለሁ” ሲል ይመልሳል፡፡
ኃይማኖት የለሹም በቀላሉ አልቀቀውም፡፡ “ዮናስ መንግሥተ ሰማያት ሳይሆን ገሀነም ቢገባስ?” ይለዋል፡፡
ያነብ የነበረው ሰውዬ ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው… “ገሀነም ከገባማ አንተ ትጠይቀዋለህ፡፡” አሪፍ አይደል!
ገሀነም ከመውረድ ይጠብቃችሁማ!
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ምን ሆነ መሰላችሁ … በዛ ሰሞን የፈረደበት ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ነው፡፡ እናላችሁ… ሴትዮዋ ሦስት ብር ከፍላ ሀምሳ ሳንቲም መልስ ስላልተሰጣት ከረዳቱ ጋር ትጨቃጨቃለች፡፡ ይሄኔ ሾፌሩ… “በቃ አትጨቃጨቅ ስጣት…” ይለዋል፡፡ ከዚያ ትንሽ ቆይቶ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ከእኛ ጋር ለስሙኒና ለሽልንግ ከምትጨቃጨቁ የቻይና ሱሪ ሺህ አምስት መቶ ብር ሲገባ መብታችሁን ለምን አላስከበራችሁም!”
(‘የጨሱ ከተሜዎች’ ቢኖሩ ኖሮ “ኧረ ቼ ጉቬራ!” ክፋቱ ሚኒባስ ውስጥ የነበርነው እንኳን ‘የጨስን ከተሜዎች’ ልንሆን… አለ አይደል… አብዛኞቻችን ከተሜነትን ‘በሚያስደንቅ ፍጥነት’ ወደ አሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን እየመለስነው ያለን ነን፡፡ ቂ...ቂ…ቂ…)
እናላችሁ… የሽልንግ ነገር ብዙ ነገር እያሳሰበን ነው፡፡ በየቦታው “ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡ (ስሙኝማ…አንድ ‘ሽልንጌ’ የምትል አሪፍ አጭር ልብ ወለድ አለች አይደል!)
እናላችሁ…ሽልንጌ የብሶታችን መግለጫ እየሆነች ነው፡፡ “ሽልንጌን!” ስንል ምጽዋት እየጠየቅን ወይም ልብህ/ልብሽ ይራራልን እያልን አይደለም፡፡ የምንጠይቀው ‘የራሳችንን ሽልንግ’ ነው፡፡ የእኛ ያልሆነ ስሙኒና ‘ዲናሬ’ ጨምሩልን አላልንም፡፡ የራሳችንን ሽልንግ ስጡን እያልን ነው፡፡ “ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡ መብታችን ነዋ!
“ሽልንጌን!” ለማለት በቻይና ሱሪ ‘ሪቮሉሽን’ ማስነሳት የለብንም!
በአገልግሎት መስጫ ቦታ ሄደን ቅሬታ ሲኖረን የምንፈልገውን ኃላፊ አናገኝም፡፡  ስሙኝማ…ይሄ እኮ ኃላፊ የማግኘት ነገር ኮሚክ ነው፡፡ አሀ…ኃላፊ ማግኘትና የመንግሥተ ሰማያት ‘ግሪን ካርድ’ ምናምን ማግኘት አይነት ነገር ተመሳሳይ እየሆኑ ነዋ!
እናላችሁ…አንዱን ኃላፊ ለማግኘት እኮ መለማመጥ፣ “እንደው በልጆችሽ ይዤሻለሁ፣ ፍቀጂልኝና ሁለት ደቂቃ ላናግራቸው!” ብለን እጥፍ ዘርጋ ማለት የለብንም፡፡ ኃላፊው እኮ አነስተኛ መንደርን ኮብል ስቶን ለማስነጠፍ ደሞዝ ‘የሚነጨው’ እኛን ለማገልገል ነው፡፡ “የቤንዚን አነሰኝ…”፣ “ውሎ አበሉ አንሷል…” ምናምን እያለ የደብዳቤ መአት የሚያጎርፈው እኛን በማገልገል ስም ነው፡፡ እና ጉዳያችንን ወደ ኃላፊ መውሰድ ‘ሽልንጋችን’ ነው፡፡ መብታችን ነዋ!
“ሽልንጌን!” ለማለት በቻይና ሱሪ ‘ሪቮሉሽን’ ማስነሳት የለብንም!
(ይቺ የኃላፊዎችን ነገር መስመሮች የጨማመርንባት በተገልጋይና በኃላፊዎች መካከል ያለው አጥር… አለ አይደል… ከሰንሰል ወደ እንጨት፣ ከእንጨት ወደ ቆርቆሮ፣ ከቆርቆሮ ወደ ብሎኬት ምናምን እያለ አሁን ጭራሹኑ…ላዩ ላይ ‘አደገኛ አጥር’ የሚል ሊሰቀልበት ምንም ስላልቀረው ነው፡፡ አለቆች ሆይ… ወደ ላይ እየራቃችሁ በሄዳችሁ ቁጥር ታች ያለነው በደንብ ስለማንታያችሁ… አሪፍ አይደለም፡፡ አሀ…ለእናንተ ብዬ ነዋ!)
እናማ…የአለቆች ነገር “ሳይጾሙ ይጸድቃሉ፣ ሳይታመሙ ይጠየቃሉ፣” አይነት እየሆነ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ኃላፊነታቸውን በቅጡ ሳይወጡ ሁሉም ነገር ለእነሱ ብቻ በሚመቻቸው ሲሆን ያው ‘ሳይጾሙ መጽደቅ’ ማለት አይደል! (እግረ መንገዴን… የሆነ ነገር ትዝ አለኝ…‘ኪሲሎጂ’ ለምንድነው ጾም የማይሆነው?…ያው እሱም ሥጋ አይደል እንዴ!)
በየቦታው ለፊርማ ደርሰው እየተጉላሉ ያሉ ሰነዶቻችንን “ኧረ ፈርማችሁ ስጡን!” ስንል “ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡ በየዝግጅቱ “ሰዓት ይከበር አታጉላሉን…” ስንል…አለ አይደል…“ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡
“ውሀ አታቋርጡብን…” “መብራት አታጥፉብን…” “ስልክ አታቋርጡብን…” ስንል… አለ አይደል…“ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡ መብታችን ነዋ!
“ሽልንጌን!” ለማለት በቻይና ሱሪ ‘ሪቮሉሽን’ ማስነሳት የለብንም!
ይቺን ስሙኝማ…ትንሽዬ ልጅ ነው፡፡ የሆነ ሰበካ ያለበት ስፍራ አባቱ ይዞት ሄዶ ልጁ የሚባለው ሁሉ ስላልገባው ስልችት ብሎታል፡፡ ራቅ እንኳን እንዳይል ደግሞ አባቱ እጁን ግጥም አድርጎ ይዞታል፡፡ ታዲያላችሁ…ልጅዬው ቀና ብሎ ሲያይ ከሰባኪው ጐን ብልጭ ድርግም የሚል ቀይ መብራት አለ፡፡ ይሄኔ አባቱን ምን ብሎ ጠየቀው መሰላችሁ… “አባዬ፣ መብራቱ አረንጓዴ ሲሆን መሄድ እንችላለን!”
በብዙ ነገር መብራቱ አረንጓዴ የሚሆንልን መቼ እንደሆነ ይነገረን፡፡
“ሽልንጌን!” ሳንል ሽልንጋችንን የምናገኝበት መቼ እንደሆነ ‘ሮድ ማፑ’ ይነገረንማ!
“ሽልንጌን!” ለማለት በቻይና ሱሪ ‘ሪቮሉሽን’ ማስነሳት የለብንም!
እናላችሁ… የ“ሽልንጌን!” ጉዳይ የሚኒባስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመብት ጉዳይ ነው፡፡ ሚኒባሶችን ከጠቀስን አይቀር ከታሪፍ በላይ እያስከፈሉን ነው፣ ተቆጣጣሪ የለም ወይ!”…ስንል አንድ ሁልጊዜ የምንሰማት ነገር አለች፡፡ “ህዝቡ ራሱ መብቱን ማስከበር አለበት፣” ይባላል፡፡ ነገርዬዋ አሪፍ ብትሆንም አሁን፣ አሁን ከ‘ወርክሾፕ ወረቀት ማሳመሪያነት’ የማታልፍ ነገር እየሆነች ነው፡፡ ልክ ነዋ… ከአንዳንድ ሚኒባስ ሾፌሮችና ረዳቶች የምንሰማቸው ዘለፋዎችና ስድቦች… አይደለም ሽልንጋችንን ኪሳችንን ውስጥ ያለውን ሁሉ ወስደው አፋቸውን በያዙልን የሚያሰኝ ነው፡፡
አሁንማ በአንዳንድ ጥቅሶችም ልክ ልካችንን እየነገሩን ነው፡፡ የምር እኮ ኮሚክ ነው…‘ፍሪ ስፒች’ በደንብ ያለበት ቦታ… አለ አይደል…ሚኒባስ የሆነ ነው የሚመስለው፡፡ በቀደም አንዱ ሚኒባስ ውስጥ ምን የምትል ጽሁፍ ተለጥፋ አየሁ መሰላችሁ… “የዓባይ ተልእኮ ስላለብን እባካችሁ ጠጋ፣ ጠጋ በሉ፡፡” እናላችሁ… “ነገ ደግሞ ምን ተብሎ ይጻፍ ይሆን!” የሚያሰኝ ነው፡፡
(ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ስላለኝ ነው… ሚኒባስ ውስጥ አንዱ ተሳፋሪ እንደው እንደ ‘ቦተሊካ’ የሚመስል ነገር ሲናገር የሌሎች ተሳፋሪዎችን ገጽታ አይታችሁልኛል! አለ አይደል…“ምን ያህል ቢከፋው ነው…” አይነት ሳይሆን… “ሂድና የሞንጎሊያ ቱሪስት ብላ!” አይነት ነገር ነው፡፡)
እናማ… በሚኒባስ ብቻ ሳይሆን በብዙ ነገሮች “ሽልንጌን!” እያልን ነው፡፡
“ሽልንጌን!” ለማለት በቻይና ሱሪ ‘ሪቮሉሽን’ ማስነሳት የለብንም! መብታችን ነዋ!
እንደገና እንኳን ለአድዋ የድል በዓል በሰላም አደረሳችሁማ፡፡ ሬይሞንድ ጆናስ የተባለ ጸሀፊ ‘The Battle of Adwa, African Victory in the Age of Empire’ በሚለው መጽሐፉ፤ እ.ኤ.አ. ‘በ1898 አሜሪካ ስፓኒሾችን ስታሸንፍና እ.ኤ.አ. በ1905 ሩስያ በጃፓኖች ስትሸነፍ፣ ስለ ግዛት ማስፋፋት ቀደም ብለው እንደ እውነታ ሲወሰዱ የነበሩ አመለካከቶችን ያናጉ ክስተቶች ናቸው ተብሎ ይወሰዳሉ፣’ የሚል ስሜት ያለው ነገር ጽፏል፡፡ ይኸው ጸሀፊ መጽሐፉን የዘጋበትን የመጨረሻ ዓረፍተ ነገር አንብቡልኝማ፡፡ (ዘንድሮ በዚቹ በእኛዋ አገር የ‘እንግሊዝ አፍ’… አለ አይደል… “እንደ ፈቺው…” ሆኗልና እንደ አፈታታችሁ ፍቷትማ! ቂ…ቂ…ቂ…)
“The signal moment for our times, the event that reopened previously settled questions for a new century, occurred not in 1905 or even in 1898. It took place in 1896 at a place called Adwa.”
የአድዋ ድል እንዲህ ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Monday, 02 March 2015 09:23

የፀሃፍት ጥግ

ኃይለኛ መፅሃፍ ለመፃፍ ኃይለኛ ጭብጥ መምረጥ አለብህ፡፡
ሔርማን ማልቪሌ
ግሩም አድርገህ እስካረምከውና እስካሻሻልከው ድረስ ትርክምርኪ ብትፅፍ ችግር የለውም፡፡
ሲ.ጄ.ቼሪ
ታሪኩ ረዥም መሆን ስላለበት አይደለም፡፡ አጭር ለማድረግ ረዥም ጊዜ ስለሚወስድ ነው፡፡
ሔነሪ ዴቪድ ቶርዩ
በህይወትህ ውስጥ ሌሎች ነገሮች ካሉህ - ቤተሰብ፣ ጓደኞች፣ ውጤታማ የሥራ ቀን - እኒህ ሁሉ ከምትፅፈው ጋር መስተጋብር በመፍጠር ድምር ውጤቱ እጅግ የበለፀገ ይሆናል፡፡
ዴቪድ ብሪን
በእኔ ልምድ እንዳየሁት፣ ታሪኩን አንዴ ከፃፉ በኋላ መግቢያውንና መጨረሻውን ሰርዞ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ እኛ ደራሲያን አብዛኞቹን ውሸቶችቻችንን የምንጨምረው መግቢያውና መዝጊያው ላይ ነው፡፡
አንቶን ቼኾቭ
እስካሁን ስኬታማ የሆንኩት ምናልባት ሁልጊዜም ስለድርሰት አፃፃፍ ምንም እንደማላውቅ በመገንዘቤና ማራኪ ታሪክን በሚያዝናና መንገድ ለመተረክ በመሞከሬ ብቻ ነው፡፡
ኢድጋር ራይስ ቡሮውስ
መጀመሪያ መሪ ገፀባሪህ ምን እንደሚፈልግ እወቅ፤ ከዚያ ዝም ብለህ እሱን ተከተለው!
ሬይ ብራድበሪ
ፀሐፊ የሚሰራበት አብዛኛው መሰረታዊ ጥሬ ነገር የሚገኘው ከ15 ዓመት ዕድሜ በፊት ነው፡፡
ዊላ ካተር
አዝናለሁ፤ የሳይንስ ልብወለድ ፀሃፊዎች ከምር ምንም ነገር አያውቁም፡፡
ፊሊፕ ኬ.ዲክ
በግጥም ውስጥ ገንዘብ የለም፤ በገንዘብም ውስጥ ግን ግጥም የለም፡፡
ሮበርት ግሬቭስ
ሰዎች ጥሩ ፅሁፍ ማግኘት አይገባቸውም፤ በመጥፎው ሲበዛ ደስተኞች ናቸው፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
ለዓመታት ምንም ሥራ ሳልጨርስ ነው የቆየሁት፡፡ ምክንያቱም አንድ ነገር ጨርሰህ ስታወጣ ትችት አይቀርልህም፡፡
ኢሪካ ጆንግ
ሌሎች ካንተ መስማት ስለሚፈልጉት ነገር ለማሰብ አትሞክር፤ አንተ ማለት ስላለብህ ጉዳይ ብቻ አስብ፡፡ እሱ ነው አንተ መስጠት ያለብህ አንድና ብቸኛ ነገር፡፡
ባርባራ ኪንግሶልቨር

Published in ጥበብ

“…ለ43 ዓመታት ያህል አስተምሬአለሁ… እንግዲህ ምን ያህል ልጆችን እንዳስተማርኩ እናንተው አስሉት… አሁን በጡረታ የማገኘው 420 ብር ነው… ምንም አይደል ይበቃኛል… ዛሬ ግን እጅግ ተደስቻለሁ… ለካስ የሚያስታውሱኝ አሉ… ይህንን ካየሁ ዛሬ ሞቼ ባድርም ግድ የለኝም…”
አንድ እለት የምፈልገውን ለመፈለግ ኮምፒዩተሬን አብርቼ ወደ Google ጎራ ስል ግድግዳው ላይ የማራቶኑን ጀግና የአበበ ቢቂላን ምስል አየሁ፡፡ Google ብዙውን ጊዜ ታላላቅ ሰዎችን ወይንም አንዳች ክስተትን ለመዘከር ይህን እንደሚያደርግ ባውቅም በእለቱ በGoogle የተዘከረው ግን የእኛው አበበ ቢቂላ በመሆኑ እየተገረምኩ የኮሚዩተሩን የመጠቆሚያ ቀስት ምስሉ ላይ አኖርኩ፡፡ Google አሁንም አልሰሰተም፤ እለቱ የኢትዮጵያዊው የማራቶኑ ጀግና የአበበ ቢቂላ የልደት ቀን መሆኑን ነገረኝ-  ኦገስት 7 1932 ወይም ነሀሴ 1 ቀን 1924 ዓ.ም፡፡ መገረሜን ይዤና “ሁለመናዬን ጆሮ አድርጌ” ዋልኩ፡፡ ማንም ስለ እለቱ ሲያወራ አልሰማሁም፡፡ ለምን? ወይ ጭራሽ ስለማናውቀው (ስላልፈለግን አናውቀውም) ወይንም አውቀነውም ግድ ስላልሰጠነው ይመስለኛል፡፡ ጥሎብን የእኛ የሆነ ነገር ያንስብን የለ! አለመታደል ይሉታል ይሄ ነው፡፡
ይህ እንግዲህ ከራቁ ገጠመኞቼ አንዱ ነው፡፡ ምን ለማለት እንደፈለግሁ እርግጥ ነው፤ገና ቀደም ተረድታችሁታል፡፡ ይህንን ማለት ድፍረት ቢመስልም አይደለም፡፡ “የእኛ ለሆኑ ነገሮች ግድ የለንም! በጣም!” ለዚህች ሀገር እጅግ የደከሙ፣ ለትውልዱ እድሜያቸውን ሙሉ የታተሩ… ታላላቅ ሰዎች አልፈዋል፤ አሁንም አሉ፡፡ የት? እነማን ናቸው? ብዙም ለእነሱ፣ ስለ እነሱ ግድ ስለሌለን አንጠይቅም፡፡ ብናውቅም እውቅና አንሰጥም፡፡ እናም የደከሙልን ቀደምቶቻችን አስተዋሽም ሆነ ተመልካች የላቸውም፡፡ ትናንትም፣ ዛሬም ምናልባትም ነገም፡፡…
እንደ ሀገርና ህዝብ አሁን ያለንበት ቦታ ላይ የደረስነው (የደረስነው የትም ይሁን የት) እንዲሁ በዘፈቀደ አይደለም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በጋራም ይሁን በግል በደከሙት ድካምና ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው፡፡ ይህንን ልብ ማለት፣ ልብም ብለንም የሚገባቸውን ክብር፣ እውቅና እና ምስጋና መስጠት አልቻልንም፡፡ በሰለጠኑት ሀገሮች “seniority” ትልቅ ክብር አለው፡፡ እንኳን የተለየና ተጠቃሽ አገልግሎት ያበረከቱ ሰዎች ቀርቶ ሌሎችም እድሜያቸው የገፋ ሰዎች በተለየ ይከበራሉ፡፡ በመሆኑም በሰዎች በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በህግ የተቀመጠ ልዩ አገልግሎትና ቅድሚያ (Priority) ይሰጣቸዋል፡፡ ለምሳሌ ባቡርና አውቶብስ ላይ በነጻ ይሳፈራሉ፡፡ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ቅድሚያ ይስተናገዳሉ፡፡… ሌላም ብዙ! ምክንያቱ ምንም አይደለም፡፡ ሽማግሌዎቹ በአቅማቸው ልክ ያቺ ሀገር የደረሰችበት እንድትደርስ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ስለሚታመን ነው፡፡
ሀገሮቹ ይህንን በማድረጋቸው የበለጠ ያተርፋሉ እንጂ ቅንጣት አይከስሩም፡፡ አንደኛ ሀገሪቱንና ትውልዱን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ያገለገሉትን ሰዎች መልሰው በማገልገላቸው የሽማግሌዎቻቸውን ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ በዚህም ሽማግሌዎቹ የሚያገኙት እርካታ አለ፡፡ በመሆኑም ለሀገራቸው በሰጡት አገልግሎት አይቆጩም፡፡ (“ይህቺ ሀገር ብዙ ብደክምላትም አሁን የት ወደቅህ አላለችኝም” የሚለውን የአረጋውያኖቻችንን ምሬት እዚህ ጋ ልብ በሉ)
ሁለተኛ የአሁኑ ትውልድም ታላላቆቹ ለሀገራቸው በመድከማቸው የሚሰጣቸውን ክብርና እውቅና ስለሚያይ እሱም ሳያመነታ የድርሻውን ለሀገሩ ያበረክታል፡፡ ምክንያቱም ሀገሩና ቀጣዩ ትውልድ ለእሱም ነገ ክፍያውን እንደማይነፍጉት ያውቃል፡፡ እንግዲህ ይህ የሚሆነው ቀደምት ባለውለታዎቻቸውን በሚያከብሩ ሀገራት ነው፡፡ ወደ እኛዋ ሀገር ስንመጣ ግን መልኩና ሁኔታው ሌላ ነው፡፡ ምናልባትም የተገላቢጦሽ፡፡ ይህቺን ሀገር በብዙ ያገለገሉትና ለትውልዱ የደከሙት ሰዎች ወዴት አሉ? ይህንን በቅጡ ጠይቀን ማወቃችንንም እንጃ፡፡
ይህቺን ሀገር በነጻነት አስከብረው ያኖሩ ጀግኖች፣ በአለም ፊት ስሟን ያስጠሩና ባንዲራዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ ስፖርተኞች፣ በረሀ ሳይሉ ጫካ ድሀ ህዝቧን ያገለገሉ ሐኪሞች፣ ለረጅም ዘመናት ጠመኔን አንቀው ትውልድን በእውቀት ያነጹ መምህራን፣ የሀገሪቱን ባህልና እሴቶች ሲያስተዋውቁ፣ ህዝቡን ሲያስተምሩና ሲያዝናናኑ እድሜያቸውን የሰዉ የኪነ ጥበብ ሰዎች… በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለዚች ሀገርና ህዝቦቿ የደከሙ ባለውለታዎቻችን ወዴት አሉ? ማንስ ያስታውሳቸዋል? በምንስ ተዘክረዋል? አጋጣሚ ፈቅዶ በየሚዲያው የሚቀርቡትን ጥቂት ሰዎች በማየት ብቻ ውለታ ቢስነታችን ምን ያህል ልክ አልባ እንደሆነ ልብ ማለት እንችላለን፡፡
እርግጥ ነው ሁሉንም ማገዝና መዘከር ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ፍላጎቱና ቀናነቱ እሳካለ ድረስ ቢያንስ ለሀገራችን እጅጉን አስተዋጽኦ ያደረጉትን ታላላቆቻችንን ማመስገን ከባድ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ገንዘብ አይደለም፡፡ ቢያንስ እውቅናን መስጠትና ማመስገን ነው፡፡
ከወራት በፊት ከአንድ ወዳጄ ጋር (ወዳጄ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም መምህር ነው) በጉዳዩ ላይ ስናወራ የነገረኝን ላንሳ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የትምህርት ተቋሙ ዓመታዊ የምስረታ በዓሉን ያከብር ነበር፡፡ የበዓሉ ኮሚቴ “የክብር እንግዳ ማን ይሁን?” በሚለው ላይ ሲወያይ ከኮሚቴው አባላት አንዱ የበዓሉ የክብር እንግዳ ለረጅም ዓመታት ያስተማሩና አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙ አንጋፋ መምህር እንዲሆኑ ሀሳብ አቀረበ፡፡ ይህ ሀሳብ በወቅቱ ጥቂቶችን ባያሳምንም በብዙዎቹ ተቀባይነት በማግኘቱ ሀሳቡ እውን ሆነ፡፡ እናም ተጋባዡ አንጋፋ መምህር በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት ተገኙ፡፡
መምህሩ በእለቱ የተሰማቸውን ስሜትና ያደረጉትም ንግግር ካለ እንዲነግረኝ ወዳጄን በጉጉት ጠየቅሁት፡፡ ነገረኝ፡፡ መምህሩ እጅግ ተደስተው ነበር፡፡ ምን አሉ መሰላችሁ? “…ለ43 ዓመታት ያህል አስተምሬአለሁ… እንግዲህ ምን ያህል ልጆችን እንዳስተማርኩ እናንተው አስሉት… አሁን በጡረታ የማገኘው 420 ብር ነው… ምንም አይደል ይበቃኛል… ዛሬ ግን እጅግ ተደስቻለሁ… ለካስ የሚያስታውሱኝ አሉ… ይህንን ካየሁ ዛሬ ሞቼ ባድርም ግድ የለኝም…”
ተመልከቱ የጉዳዩ አስኳል ገንዘብ አይደለም፡፡ እውቅና እና ምስጋና ነው፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ ያገለገሉንን በሀገር ደረጃ ማመስገን ቢከብደን እንኳን በየመስካችን እንችላለን፡፡ ምን በዚህ ብቻ “ከአንጀት ካለቀሱ…” እንዲሉ አበው፣ ሌሎችም ብዙ አማራጮች ሞልተዋል፡፡ እስከፈለግን ድረስ ከባድ አይደለም፡፡
ታዲያ ጉዳዩ ይህንን ያህል ቀላል ከሆነ ለምን መፈጸሙ አቃተን? ምክንያቶቹ በርካታ ይመስሉኛል፡፡ አንድ ሁለቱን ልጥቀስ፡፡ ቀዳሚው ነገር ታላላቆቻችንን ማድነቅ ባህላችን ስላልሆነ ነው፡፡ እንደ ህዝብ እጅጉን ከምንቸገርባቸው ነገሮች አንዱ ከልብ ማድነቅ አለመቻላችን ነው፡፡ ለምን እንደሆነ በቅጡ ባይገባኝም (ምናልባት ሌሎችን ስናደንቅ እኛ ዝቅ የምንል ስለሚመስለን ይሆን?) አለማድነቅ ችግራችን ነው፡፡ የምር ከማድነቅ ይልቅ ከአንገት በላይ ማንቆለጳጰሱ ይቀናናል፡፡ ከልቡ ማድነቅ የማይችል ደግሞ ታላላቆቹን ሊያከብር፣ ለዋሉለት ውለታም ሊያመሰግን አይችልም፡፡
ሌላው ምክንያታችን ደግሞ ሰዎቹ ካበረከቱት አስተዋጽኦ ይልቅ ለነበራቸው (ላላቸው) አስተሳሰብ፣ ለተወለዱበት ብሔር ወዘተ… ትኩረት ስለምንሰጥ ነው፡፡ “እሱ እኮ እንዲህ ነበር” ወይም “እንዲህ ነው” ማለት ይቀናናል፡፡ አስተሳሰባቸውንና ማንነታቸውን ከአስተዋጽኦዋቸው መለየት አንችልም፡፡ እናም ብዙዎችን በማንነታቸው ብቻ እንገፋለን፤ ገፍተናልም፡፡ የዘከርናቸውን ጥቂቶችንም የዘከርነው ካበረከቱት አስተዋጽኦ ይልቅ የነበራቸውን ማንነትና አስተሳሰብ እንዲሁም አባል የነበሩበትን ቡድን መለኪያ አድርገን ነው፡፡
ይህ አመለካከት የብዙዎችን ክብርና ምስጋና ነፍጎአል፡፡ አንድ ግለሰብ መመስገንና እውቅና ማግኘት ያለበት በስራው ሊሆን ሲገባ ማንነቱና አስተሳሰቡ ተመዝግቦ ውለታው አፈር ይለብሳል፡፡ የዚህ አመለካከት ጉዳቱ ከዚህም ያልፋል፡፡ በርካታ የሀገር ባለውለታዎችን ከሀገር አሰድዷል፤ ከዚህ የተረፉትንም እንጀራ አሳጥቶአል፡፡
የሀገርና የህዝብ ባለውለታዎችን አለማመስገንና እውቅና አለመስጠት ሞራላዊ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሀገራዊ ጉዳቶችን የሚያስከትል በመሆኑ ግዴታም ነው፡፡ አንዱ ጉዳቱ ትውልድን አለማነሳሳቱ ነው፡፡ ባለውለታዎችን የማታከብርና የማታመሰግን ሀገር ቀጣይ  ባለውለታዎችን አትፈጥርም፡፡ በፍጹም! “ደግሞ ለዚች ሀገር…” የሚል ቃልን በምሬት የሚናገሩ ሰዎች አጋጥመዋችሁ አያውቁም? እነዚህ ሰዎች እንዲህ ማሰባቸው ልክ ነው ባልልም መነሻ ግን አላቸው፡፡ ሀገሪቱ የደከሙላትን ዞር ብላም እንደማታይ ያውቃሉ፡፡ ይህ ተስፋ አስቆርጦአቸዋል፡፡ እኔስ ነገ አሰኝቶአቸዋል፡፡ ጉዳቱ ሀገርን ትጉህ ተረካቢ እስካማሳጣት ይደርሳል፡፡
ሌላው ጉዳት አዲሱ ትውልድ ሊከተላቸውና ሊማርባቸው የሚገቡ ሀገራዊ አርአያዎችን ያሳጣል፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ ብዙዎቹ የዘመናችን ህጻናት የሚያደንቋቸው ታላላቅ ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡
ምክንያቱም ሊከበርና ሊመሰገን የሚገባውን አክብረንና አመስግነን አላስተዋወቅናቸውም፡፡ እናም በቅርቡ ያገኙትን አርአያ ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ እጅጉን ትጉህ የሆኑት የውጪ ሚዲያዎች በሚያከብሩአቸውና በሚያደንቋቸው ግለሰቦች የእኛን ልጆች ልብ ቅኝ ይገዛሉ፡፡
የእኛን ቀደምቶች ለማስታወስ ዳገት የሆነባቸው የሀገራችን አብዛኞቹ ሚዲያዎችም ለዚህ ትጉህ ናቸው፡፡ የውጪውን ዓለም ስፖርተኛ በሉ ተዋናይ፣ ሙዚቀኛ በሉ ቢሊየነር… የህይወት ታሪኩን ብቻ ሳይሆን እስከሚወደው ምግብና አለባበስ ሳይቀር አብጠርጥረው ይነግሩታል፡፡ በዚህም ህጻናቱ ሀገራዊ አርአያዎችን በማጣታቸው ከሀገራቸው ታላላቅ ሰዎች ሊማሩአቸው የሚገቡ የሀገር ፍቅር፣ ስነምግባር፣ ታሪክና በርካታ እሴቶችን ያጣሉ፡፡
ሀገርና ትውልድ የሚገነቡት በቅብብሎሽ ነው፡፡ በዚህ ቅብብሎሽ ውስጥ ደግሞ ታላላቅ አስተዋጽኦዎችን የሚያደርጉ የሀገርና የትውልድ ባለውለታዎች አሉ፡፡ እነዚህ የሀገር ባለውለታዎች የራሳቸውን ግላዊ ጥቅም ለሀገርና ለትውልድ እስከመስጠት ድረስ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ እነሱን ማመስገንና ለአስተዋጽኦዋቸው እውቅና መስጠት ሀገራዊም ህዝባዊም ግዴታችን ነው፡፡ ይህን አለማድረግ ጉዳቱ ያህላል የለውምና፡፡
መልካም ሰንበት!!

Published in ህብረተሰብ

(እውነት አንድ)
ኮንዶሚንየም ደረሰኝ
ባለ ሶስት መኝታ ቤት ሰሚት አካባቢ ዕጣ ወጣልኝ፡፡ ቻው ድህነት፣ ቻው መንገላታት፡፡ አሁኑኑ በጂፕሰም አሰማምሬ አከራየዋለሁ፣ በደህና ዋጋ፡፡ ደሞ ሰፈሩ ፀዴ ሰፈር ነው፣ ባቡርም እየገባበት ነው…..
መንግስት ዘንድሮ ከምር ጸደቀብኝ፣ ይመቸው፣ ባሁኑ ምርጫ እመርጣቸዋለሁ፤ ኧረ ለዘላም ይኑሩ!! ያ ቀውጢ ደጋፊ ጀለሴ እኮ የሚናገረው እውነቱን ነው…… ምን ነበር ያለኝ? “…የኛ አገር ተቃዋሚ ማለት ምቀኛ፣ ጨለምተኛና ዘረኛ ነው፡፡ ከላይ ነው አንድነት ምናምን የሚሉት፤ ሲፎግሩ ነው……ሁሉ ነገር ላይ ሲያማርሩ ሲነጫነጩ ይደብራሉ…የቦሌ መንገድ ሲሰራ፣ ባቡር ሲሰራ --- ትራፊክ ጭንቅንቅ በዛ፣ ኡኡ.. ይላሉ…. ባህላቸው ነው፡፡ ትልልቅ የመብራት ፕሮጀክቶች እንዳልተመረቁ ሁሉ መብራት ሲጠፋ ያብዳሉ…” (አሪፍ አንግሊዝኛ ሁላ ተጠቅሟል፡ ‘form እንጂ substance የላቸውም፤ ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ ሲሉ ለይስሙላ ነው፣ ባለፈው የታሪክ ጠባሳችን ምክኒያት ኢትዮጵያዊነት እንዳይሰማቸው የተደረጉ ብዙሃን ህዝቦችንና ብሄረሰቦችን ሆነ ብለው ረስተው ነው፣ በአፋቸው የሚያወሩት ሌላ በተግባራቸው ደግሞ ትምህክተኛና ናቂዎች ናቸው…ይሄ የCentrists መገለጫ ነው…በባዶ ኡኡ ማለትና ማስመሰል ነው እሚወዱት’)
እውነቱን ነው…. ያምሃል እንዴ? ቤት ሰጠኝ እኮ ጸሀዩ መንግስታችን፣ ምን እፈልጋለሁ ሌላ!?... የእድገት ውጤት እኮ ነው፡፡ አዳሜ በየሰበብ አስባቡ ከጎረቤት ጋር እንዳልተጨቃጨቀች ዛሬ አኗኗሯ ተለወጠ፣  ተሻሻለ፡፡ አሁን እንደው ምቀኛ ካልሆንክ “አላደግንም” ብለህ ትገግማለህ?……ሰዉ ጨለምተኛ ነው …አሁን ኢቢሲ ስለ ልማት እና ስለ እድገት ስላወራ ይጠምዱታል፣ …እውነት ስለተናገረ እኮ ነው፣ ሌላ ምንም አይደለም….እኔ ‘ኮ ግርም የሚለኝ በደርግ ጊዜ ወጣት ተገድሎ ለጥይት እንዳልተከፈለ፣ እሱን ሙልጭ አድርገው ክደው ‘የማውራት ነጻነት አሁኑኑ!’ ይላሉ፡፡ ተቃዋሚዎች… ይሄ ክህደት ነው፤ ክፋት እና ጨለምተኝነት እኮ ነው፤ ሌላ ምንም የለም….
በጎ አለመመኘት እኮ በሽታ ነው፣ ስለ ምንም ነገር በጎ አለማውራት እኮ የአእምሮ ችግር ነው፡፡ ለውጥ የለም፣ መሻሻል የለም ብሎ መገገም ክፋት ነው፡፡ አባይ ግድብ ላይ ማሾመር፣ ማጣጣል ክፋት ነው፡፡ አለም የመሰከረለትን የትምህርትና የጤና ሽፋንን እንዳላዩ ማለፍ በገበሬ ቤተሰብ ላይ ማላገጥ ነው፣ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ ቢያንስ አለም ያመነውን  እድገት መካድ፣ ያለውን መሻሻል እንዳላዩ ሆኖ በትናንሽ ስህተቶች መጮህ ክፋት ነው፡፡ ለማንኛውም ኮንዶሚኒየም ደርሶኛል፡፡
መንግስት ይመቸው፤ ለዘላለም ይኑር!
(እውነት ሁለት)
ኮንዶሚንየም አልደረሰኝም
ስፎግራችሁ ነው፣ ኮንዶሚኒየም አልደረሰኝም- ወፍ የለም፡፡ ዕጣውን አፍጥጬ ሰባቴ ሸመደድኩት፣ የለም፤ በቃ የለም፣ ዕድሌ ነው፡፡
ቆጨኝ፣ ከምር ቆጨኝ ያ ጉዳይ ገዳይ እኮ ነግሮኝ ነበር፣ አላምን ብዬ ነው….ለነገሩ ያረጋል አይሸሹም ጋማ ከተባለበት ቢዝነስ (ሙስና) አንዱ ‘ባለ አንድ መኝታ ኮንዶሚኒየም በስሙ አለው፣ ከየት አመጣው?’ ተብሎ ነው (ልክ ድንገት ያወቁበት አስመሰሉት)……እና አሁንስ እጣው እንዳልታፈነ ምን guarantee አለኝ? ምንም…..መንግስት አሁንስ አበዛው፣ ከምር አዝግ ነገር ሆነ! እምልህ የማማረር ሙድ ለማራመድ ሳይሆን ግራ ሆኖብኝ ነው፡፡ መብራት ጠፋ፣ ወይንም እኛ ሰፈር ውሃ ከጠፋ 2 ወር አለፈው ብዬ እሪሪሪ አልልም፡፡ ግን አለ አይደል፣ ዜና ላይ ዝም ብሎ ሰበብና አባባል መዘብዘብ ይመራል፡፡ በዝቶ የሸመደድከው ሰበብ፡
“መብራት የሚጠፋው ትራንስፎርመሩ ከአቅሙ በላይ ስለሆነ ነው”
“ሞባይል የማይሰራው ኔትዎርኩ የZTE ስላልሆነ ነው”
“ዘይት የጠፋው አንዳንድ ሃላፊነት የማይሰማቸው የመሃከለኛው መደብ አመራር አባላት የአመለካከት ጥራት ስለጎደላቸውና እና ካንዳንድ ደላላዎች ጋር ተገቢ ያልሆነ የNetwork ሠንሠለት ስለፈጠሩ ነው፡፡”
እና ምንድነው መላው?
 “….ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየጣርኩኝ ነው….” (አባባሉ ሲሰበሰብ ይኸው ነው)
….ያ ተቃዋሚው ጀለሴ ለካ እውነቱን ነው፡፡ “ዘንድሮም ደርግ ሲሉ ሼም የላቸውም፤ 20 አመት አለፈ እኮ ደርግ ከጫረ…አለም ተገለባብጦ ተቀይሯል እኮ፡፡ …ቆይ አሁን…. ‘ጫማ የለኝም ብለህ አትጨናነቅ እግር የሌለው አለና’ ብሎ ፍልስፍና ምንድን ነው?….ልማት ማለት ምን ማለት ነው?….‘ቡናኔ ወረዳ ውስጥ የህዝብ ሽንት ቤት ተመረቀ’ የሚልን ዜና ምን ትለዋለህ?......ኢቢሲ ሙድ እየያዘብን ነው እንዴ? ለመሆኑስ እስከ ዛሬ የት ነበሩ ? ሁሉ ነገር ከተጀመረ እኮ ቢበዛ 6 አመት ቢሆነው ነው…
 አደግን አላደግን አይደለም እኮ ዋናው ጉዳይ፡፡ እድገቱን እነ ማን ጠርንፈው ወሰዱት ነው ጥያቄው……ግልጽ እኮ ነው…፡፡ 100 ገበሬ ሚሊየነር ሆነ ተባለ፤ እውነት ብለን እንውሰደው፣ ግን ደግሞ 10 ሚሊዮን ገበሬና ልጆቹ ደግሞ የፈረንጅ ስንዴ ይረዳሉ፣ዘንድሮም ማለት ነው፣ እና አስረዳኛ ለውጡን…፡፡ ገበሬውስ ወይ ስንዴ ይረዳል፣ ወይንም በSaftey Net ይታቀፋል…የከተማ ድሃውስ….የአስኮ መንገድ አለቀ አላለቀ ለእትዬ ሽታዬ ምኗ ነው?! በቆሎ በኪሎ አንድ ብር ቢቀንስ ግን ተመስጌን ትላለች….ከተማ እየኖርክ በዚህ ኑሮ ውድነት መውለድ እኮ ትልቅ crime ነው፣ ባንተም ላይ በልጅህም ላይ….. ግፍ እንደሰራህ ቁጠረው…
(ቀጠለ ጀለሴ) “……ትልቁ ችግራቸው እኮ አይሰሙም፤ ማንንም፡፡ ጥሩም ሰርተው ንግግር  አይችሉበትም፤ ሰው አያማክሩም፡፡ አሁን በቀደም እኛ ሰፈር እነ ፋዘርን ጠርተው ‘የመለስን ራዕይ ለማሳካት ምን ማድረግ አለብን?’ ብለው  ውይይት አካሄዱ፡፡ ፋዘር ማታ ላይ ‘ኧረ እነዚህ ሰዎች ምን ሁነው ነው እሚያላግጡት?’ ብሎ ሲያብድ አመሸ፡፡ እሱ ደግሞ ታውቀዋለህ መለስን ይወደዋል፣ ያከብረዋል፡፡ ግን እንዲህ የሰፈር ወረኛ እና ካድሬ በመለስ ስም ሲያላግጥ ይሸማቀቃል፡፡ ታ’ቃለህ እስታሊን፤ “ሌኒን እንዳለው--” እያለ ነው አንቀጥቅጦ ሶቪየትን የመራት… አሁኑም ሙዱ ያው ነው…”
(አሁንም ቀጠለ) “ሰዉ የመናገር ነጻነት ሲል ያስቀኛል፣ ይገርመኛል…እኔ ግን ‘ምመርጠው፣ ‘ያለ ማሰብ፣ ሌላውን አለም ያለማየት፣ የመደደብ መብት ይከበር’ ነው ‘ምለው-- ከምሬ እኮ ነው…ባታይ፣ ባታስብ፣ ባታወዳድር፣ ባ’ታቅ እኮ አትናደድም፣ ኡኡ አትልም፡፡ ጸረ ሙስና ምናምን ሲባል ያስቀኛል…..አሁን የት የት እና እንዴት እንደሚጨረብ ለማወቅ እኮ እድሜ ነው እሚፈልገው፤ ከ18 አመት በላይ ከሆንክ በቂ ነው፡፡ ምን ድብቅ ሚስጥር አለ?...”
“…አበሻ ደግሞ ቀበሮ ነው፤ እያወቀ እንዳላወቀ ያጨበጭብልሃል፣ ልቡን አታውቀውም፣ እንኳን ለመንግስት ለሚስቱም የልቡን አያወራም፤ ላሽ ነው እሚልህ….. ልክ ስትፈርጥ ‘እኔም ብዬ ነበር’ ይልሀል፤ ከዚያ ወዲያው ይረሳሃል..ሙሰኛ ተብለህ ብትታሰር፣ሽብርተኛ ተብለህ ብትታሰር፣ብትፈታ፣ ካገር ብትለቅ፣ ብትመለስ፣ብትሾም፣…ዝም ነው ሚልህ…. እንዳላየ ኳስና ድራማ ያሳድዳል…ነገ መንግስት ቢወድቅ፣ ሰዎቹን ጊዜ ቢጥላቸውም ያው ነው…ሁለት ሳምንት ያወራና ይረሳዋል…እኔ ግን እፈራለሁ፡፡
አንዳንዴ የእነሱም ነገር ደስ አይለኝም--- ከኛ በላይ ላሳር አይነት ነገር ነው!
(እውነት ሶስት)
እውነት  ምንድነው?

 “--አስራ አንዱ የክስ መዝገቦች፤ አስራ አንዱ ክርክሮች፤ አስራ አንዱ ቅጣቶች፣ አስራ
አንዱ ትረካዎች የሚነግሩን ባለዲሞትፎር ድሮም ችሎት እንደማያምርበት ነው፡፡--”

የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ The case of the Socialist Witchdoctor  የ22 አጫጭር ትረካዎች መድበል ሲሆን ትረካዎቹ በሁለት ክፍል ተለይተው ቀርበዋል፡፡ በክፍል አንድ አድራሻቸውን ፍርድ ቤት ያደረጉና በክስ መዝገቦች፤ በክርክሮች፤ በጥፋተኝነት እና በቅጣት ውሳኔዎች ላይ የተመሰረቱ አስራ አንድ ትረካዎች እናገኛለን፡፡ ትረካዎቹ አንድም አስራ አንድም ናቸው፡፡ አንድነታቸውንም አስራ አንድነታቸውንም በኋላ እመለስበታለሁ፡፡
በክፍል ሁለት እንደዚሁ አስራ አንድ ትረካዎች እናገኛለን፡፡ እንደ መጀመሪያው በአንድ ቦታ የሚከናወኑ አይደሉም፡፡ ስለዚህ እነዚህን አንድም አስራ አንድም ናቸው ማለት ባይቻልም ፍጹም አይመሳሰሉም ደግሞ ማለት አይቻልም፡፡ በግድ አንድ ለማድረግ ሳይሆን፤ እንቅልፍ በሚያሳጣ ጸጉር ስንጠቃም ለመለያየት ሳይሆን በዚህ በሁለተኛው ክፍል ውስጥ ከተዘረዘሩት ትረካዎች መካከል በአንደኛው ማለትም “በሽብር ሚዛን አስር” መግቢያ ላይ የምናገኘው ኃይለ ቃል የቀሩትን ትረካዎች የጋራ ፍሬ ነገር በማስረዳት ረገድ ለጥቅስ የሚበቃ ይመስላል፡፡ እንዲህ ይላል፡--
ትረካ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመራጭ የጊዜ ማሳለፊያ ቢሆንም፤አሁንም ጥቂት ተጠራጣሪዎች ከሰማኒያ በመቶ በላይ መሀይም ባለበት አገር ውስጥ ድሮም ሌላ አማራጭ ሊኖር አይችልም በማለት ይናገራሉ፡፡ ለማንኛውም በዕድሜ የገፉ ሰዎች የተካኑበት ትረካ በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ሁኔታ እንደተለወጠ የማይስማማ የለም፡፡
በአሁኑ ጊዜ አሰቃቂዎቹና አስገራሚዎቹ ታሪኮች የሚተረኩት በሽማግሌና ባልተማሩ ሰዎች ሳይሆን በተማሩ ወጣት ካድሬዎችና መገናኛ ብዙኃን ተብሎ በሚጠራው አካል ነው፡፡ በድሮ ጊዜ በአጠቃላይ ታሪኮች ለዘብ ያሉና ልጆችን ለማስፈራራት ያህል መጠነኛ ምትሀታዊ ጉዳዮች ያሉባቸው ነበሩ፡፡ ስለሚያወሩ ጥንቸሎች፤ስለ ሸረኛ ጦጣዎች፣ ስለ ታላላቅ አናብስት፤ስለ ተንኮለኛ ጅቦች፤ የተለመደውን አጭበርባሪ እባብ ሳንረሳ በአጠቃላይ ጉዳት አልባ ታሪኮች ነበሩ፡፡
አሁን አሁን ግን አብዮቱ ምስጋና ይግባውና ታሪኮቹ ስለ ሰዎች ሲሆኑ ፈጣሪ የሚባል ከተጠቀሰ ያው ሰማያዊውን አምላክ የተኩትን እኚያን ምድራዊ ጥበበኛ ሰው ለመግለጽ ነው ማለት ነው፡፡ እሳቸውም ስማቸው የተባረከ ይሁን ሊቀመንበር ተብለው ይጠራሉ:: (263)
   ከአብዮት በኋላ ትረካ ተቀየረ ማለት ተያይዞ ሌላም ነገር ተቀይሯል ማለት ነው፡፡ ለውጡ ምን አይነት ነው? አንድ ጥያቄ ነው፡፡ አለዋወጡ እንዴት ነው? ደግሞ ሌላ፡፡ በዚህ የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ መድበል ሁለተኛው ክፍል ውስጥ የምናነባቸው አስራ አንድ ታሪኮች፤ በአብዮት ምክንያት ስለምናገኛቸው አዳዲስ አልፎ አልፎም እንግዳ የኅላዌ ሁኔታዎች(existential situations) ይነግሩናል፡፡ አያይዘውም እስከ አብዮቱ ዋዜማ የዘለቁት የቀድሞ ኅላዌ ሁኔታዎች ምሰሶና ማገር የነበሩት ሕግጋት፤ ደንብ፤ ባህል፤ትውፊት፤ ነውር፤ የሙያ ስነ ምግባር ወዘተ፤ የአገልግሎት ዘመናቸው እንዳበቃ በአስደንጋጭ መልኩ ይተርኩልናል፡፡
የአብዮተኞች ሕልም በተለያዩ ምክንያቶች (ባለመታደል ወይ ባለመታገል ሊሆን ይችላል) ወደ ቅዠት የተቀየሩ እንደሆነ አዲሱና እንግዳው የኅላዌ ሁኔታ አስፈሪም አስደንጋጭም ይሆናል፡፡ የአብዮት ህልም ቅዠት ሲሆን የሰው ልጅ በተፈጥሮ አምባገነንነት ምክንያት ሳይሆን፤በራሱ ውዴታና ግዴታ ከሞትና ከጥፋት ጋር በየቅጽበቱ ይፋጠጣል፡፡ በሁለተኛው የመድበሉ ክፍል ውስጥ የምናገኛቸው የበቀል፤የክህደት፣ የክፋት፤የጭካኔ፣ የተስፋ መቁረጥ እና የሰቀቀን ታሪኮች የአዲሱ ኅላዌ ሁኔታ መገለጫዎች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ በቀል፤ክህደት፣ ክፋት፤ጭካኔ፣ ተስፋ መቁረጥ እና ሰቀቀን በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ ያሉ፤የነበሩና የሚኖሩ ናቸው ሊባል ይችላል፡፡ ለክርክር ማጠናከሪያም የተለመዱት የአቤልና የቃየል፤የኢየሱሰና የይሁዳ፤ የነብዩ መሀመድና የቁራይሽ አሳዳጆቻቸው ታሪክ በምሳሌነት ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ መጽሀፍ እንደምናነበው በቀል፤ክህደት፣ክፋት፤ጭካኔ፣ ተስፋ መቁረጥ እና ሰቀቀን ሰብሰብ ብለው፤እንደውም ተደራጅተው የምናገኛቸው የአብዮት ሕልም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ቅዠት ሲቀየር  በሚፈጠረው አዲስ የኅላዌ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም አብዮት የሰው ልጅ ሕይወት ናሙና ነው ማለት ይቻላል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ሰርቶ ማሳያ!
ሰብሰብ ብለው የምናገኛቸው እነዚህን የሰው ልጅ ክፉ ዕጣ ፈንታዎች ብቻ አይደለም፡፡ ከድርሰቱ ይዘት ሌላ ቅርጹም ራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ አጫጭር የሆኑት ትረካዎች ቀልብ የሚስቡት ትንግርታዊ አጋጣሚዎች ተደራጅተው ታጭቀው ስለቀረቡ ይመስላል፡፡ ባለታሪኮቹ ብዙ ጊዜ ባልጠበቁትና በጠበቁት ሁኔታም ጭምር የቅርብ ሰዎቻቸው ዕጣ ፈንታ ይከተላቸዋል፤ ወይም ይከተሉታል፡፡ ድንገት በውድቅት በትንሳኤ ዋዜማ በህመምተኛ ቤት ዘው ያለ ሽምቅ ተዋጊ፣ሆስፒታል የቁስለኞችን ህይወት ታድጎ ለሌላ ዙር ግርፊያና ግድያ የሚያቀብል ሀኪም፣ የገዛ ልጆቹና ወዳጆቹ የአብዮት ዘመን ተቃርኖአዊ አሰላለፍ ውስጥ የገቡበት አባት ወዘተ--፡፡ በትረካዎቹ ውስጥ  ባለታሪኮቹ  አፍንጫቸው ስር ባለው ጉድ ወይም እድል በመታጠራቸው ትልሞቹ ተለዋዋጭ፤ ያልተጠበቁና ወይም የሚጠበቁ ቢሆኑ እንኳን የሚቆረቁሩ ፍጻሜ አዝለዋል፡፡ በደፈናው በሁለተኛው ክፍል የተካተቱት አስራ አንድ ትረካዎች በአብዛኛው ጠላት ከሩቅ አይመጣም ይሉናል፡፡ ሰው ለሰውም ይላሉ፡፡ በዚህ መጽሀፍ የኢትዮጵያ ማህበራዊ ስነ ልቦና ሰብሰብ ተደርጎ ተጠርዟል፡፡
በሁለተኛው ክፍል ከተተረኩት አጫጭር ልቦለዶች አንዳንዶቹ ታሪክ ቀመስ ወይም በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን የሚጠቁሙ ምልክቶች ስላሉ፤ በፈጠራ ድርሰት ውስጥ በምናባዊነት ምክንያት አንድ ደራሲ ለወትሮ  ይጎናጸፋቸው የነበሩ የደራሲ ልዩ ፈቃዶች(poetic licenses) መወሰናቸው አልቀረም፡፡ ትረካ ከሕይወት ቢቀዳም ካንድ ታሪካዊ ግለሰብ ገጠመኝ በቀጥታ ሲገለበጥ፤ በዚያ ላይ ደግሞ ኋላ ላይ እንደማወሳው የትረካዎቹ ዘውግ ፖለቲካዊ ሥላቅ ሲሆን ወጎቹ አከራካሪ ሆነው ስነ ምግባራዊም፤ ፖለቲካዊም ጥያቄ ሊቀርብባቸው ይችላሉ፡፡ እናም በእውን የነበሩ ሰዎችን ገጠመኝ የትረካው አካል በማድረጉ ድርሰቱ ለምን ዓላማ ተዘጋጀ የሚል ጥያቄ ሊነሳበት ይችላል፡፡             
በመጀመሪያ ክፍል ስላሉት አንድም አስራ አንድም ትረካዎች እንመለስ፡፡ አንድ ያደረጋቸው መቸቱ ፍርድ ቤት መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይ ዝምድናቸው በትረካዎቹ ዘውግ ምክንያት ነው፡፡ ሁሉም ሥላቅ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ሥላቅ! ያስቃሉ፤ ያዝናናሉ፡፡ ሥላቅ ከኮሜዲ በምን ይለያል? ጥያቄው ይሄ ነው፡፡ አስቂኝ ጥበባዊ ስራዎች ግባቸው ብዙ ጊዜ መነዝነዝ ሳይሆን ዘና ማድረግ ነው፡፡ ሥላቅ ግን ከሳቁ መልእክቱ ይበልጥብኛል ይላል፡፡ መሳለቂያው ግለሰብ፤መሳለቂያው ቡድን፤መሳለቂያው ተቋም፤ መሳለቂያው መንግስት ሊሆን ይችላል፡፡ በአድራጎቱ እና በጉራው መሀል ያለው ጭልጥ ያለ እፍረተ ቢስነት ታዛቢን ስለሚያናድድ መሳለቂያውን በአሽሙር፣ በቅኔ፣በሽሙጥ በማሳነስ እስከ ዶቃ ማሰሪያው ልክ ልኩን በመንገር እንዲታረም ማድረግ ነው፡፡ ታዲያ ሥላቅ ውስጥ ሳቅን ምን አመጣው ከተባለ፤ ማሽላ እያረረ ይስቃል ይላል ሀበሻ!  
ሥላቅ በሰው ልጅ ነባራዊ ሁኔታዎች እና ኀሊናዊ ሁኔታዎች መካከል እርቅ ሳይኖር ሲቀር እንደሚከሰት ፈላስፎቹ ይነግሩናል፡፡ እሳት በሌለበት ጭስ እንዳይጨስ፤ ጉድለት በሌለበትም ሥላቅ የለም ሊባል ይችላል፡፡ ስለዚህ ከያንዳንዱ ፖለቲካዊ ሥላቅ በስተጀርባ ፖለቲካዊ ጉድለት አለ፡፡ በሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ የፖለቲካ ሥላቁ የሚጀምረው የደርግ መንግስት ነጻ እርምጃን ገንዘቡ በማድረግ የሽብርና የጭካኔ የተመሰከረለት ባለንብረት ሆኖ ሲያበቃ  ፍርድ ቤት ያማረው፤ ሞራላዊ ፕሮፓጋንዳም የዳዳው ጊዜ ነው፡፡ አስራ አንዱ የክስ መዝገቦች፤አስራ አንዱ ክርክሮች፤ አስራ አንዱ ቅጣቶች፣ አስራ አንዱ ትረካዎች የሚነግሩን ባለዲሞትፎር ድሮም ችሎት እንደማያምርበት ነው፡፡ ዳኛ አይተንፍሱ ሙጬ የጦር ሰራዊት ሻለቃ  ነው፤ ከኦጋዴን መድፈኛ ክፍለ ጦር በሊቀመንበሩ ፍላጎት በቀጥታ በአንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ላይ ተሰይሟል፡፡ ሥዩመ እግዚኣብሄር በሌለበት ያው ሥዩመ መድፍ ነው እየሰራ ያለው፤ሥዩመ ሕዝብ ገና ሩቅ ይመስላል፡፡ አቃቤ ህጉ ሲቪል ሲሆን፤ ተከላካይ ጠበቃው የጦር ሰራዊት መቶ አለቃ ነው፡፡ በትረካዎቹ መሳለቂያው ባብዛኛው የደርግ መንግስት ነው፡፡ የሰራውን ሰርቶ ሲያበቃ ያም ያነሰ ይመስል መድፍ ስለተያዘ ብቻ ሊደረስበት በማይቻለው ሞራላዊ ማማ ላይ ለመውጣት የሚያደርገው ሙከራ ዋጋ ቢስ እንደሆነ፤ መዘባበቻም እንደሆነ፤ መታረምም እንዳለበት ታሪኮቹ ያስረዱናል፡፡     
አስራ አንዱን ትረካዎች  የፍርድ ቤት መቼትና የፖለቲካ ስላቅ ቢያዛምዳቸውም የየራሳቸው የኋላ ታሪክና ዕጣ ፈንታ ያላቸው አስራ አንድ ባለታሪኮች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ ቀበሌ ደጃፍ ባለማወቅ መሽናት ልክ በቤተ እምነት አካባቢ እንደ መጸዳዳት ነውርም ወንጀልም ሆኖ ይተረካል፡፡ እንዲሁም አንድ ጀብደኛ ገራፊ የተገራፊዎቹ ቁጥር በማነሱ ብስጭት ገብቶት የፈጸመው ወንጀል ይነገረናል፤ የገራፊው ብስጭት ምሉዕ ይሆን ዘንድ ቅጣቱ የሱን ደንበኞች ቁጥር (ተገራፊዎቹን) ማሳነስ ነው! ለገራፊው ከዚህ በላይ ቅጣት የለምና ይቆረቁረዋል፤ያሳብደዋል፡፡ ምነው ቢባል በዘመኑ አዲስና እንግዳ የኅላዌ ሁኔታዎች (existential situations) ተፈጥረዋል፡፡ ሺህ ጊዜ እንግዳ የኅላዌ ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ትረካዎቹ ግነት አያጣቸውም፡፡ ነገር ግን ግነት አንዱ የስላቅ ዘዴ ነውና እንታገሰዋለን፡፡ ግነት አላማው ጉድለቱን ማሳየት በዚያውም ሳቅ ማጫር እንጂ ጉድለቱን ማስፋት አይደለም፡፡      
ደራሲው ሀማ ቱማ በዚህ የፖለቲካ ሥላቅ ትረካዎቹ፣ በአብዮቱ ማግስት ስለተፈጠሩት የፖለቲካ ጉድለቶች ሲያሳየን እንደ ዲሞትፎር፣ እንደ መድፍ፣ እንደ ብር ሁሉ ቋንቋ ፤ትረካና ሞራል ኃይል ያላቸው መሳሪያዎች እንደሆኑ ያመላክተናል፡፡ ሚሼል ፎኮ የተባለ የሀያኛው ክፍለ ዘመን የፈረንሳይ ሊቅ፤ ኃይል የትም ቦታ አለ፤እናም አደገኛ ነው ይላል፡፡ የእሱን እይታ ስንተረጉመው ኃይል በቤተመንግስት፤በጦር ካምፕ እና በባንክ ቤት ታጭቆ የመሰብሰቡን ያህል ሰው ባለበት ሁሉ ደግሞ ዘርዘር ብሎ ይገኛል፡፡ ቋንቋና ትረካ፤ ትረካና ሞራል እንዲሁም ሥላቅ በቀላሉ የሚታዩ ኃይል አይደሉም፡፡ እነዚህ የተቃውሞ መሳሪያ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አብዮት የተለኮሰው ነባራዊና ሕሊናዊ ሁኔታ የተሟላ ጊዜ ነው ይላሉ፤አብዮተኞቹ፡፡ ለኅሊናዊው ሁኔታ መፈጠር የተማሪዎች እንቅስቃሴ  ወሳኝ ቦታ ነበረው፡፡ ተማሪ በመጀመሪያ እና በአብዛኛው የታገለው በጽሁፍ ነበር፤ በቋንቋ! የበታች ወታደሮች ደግሞ እድሜ ለስራ ድርሻቸው ስልጣንን በዲሞትፎር ወሰዱ፤ በዲሞትፎርም ጠበቁት፡፡ ትንቅንቁ ቀጠለ፡፡ ሁሉም ባለው አጠቃ፤ ተከላከለም፡፡ ውጤቱ የታወቀ ስለሆነ አልዘረዝረውም፡፡ መጀመሪያ ላይ የነበረው በቋንቋ፤ በጽሁፍ የመታገል ነገር በኋላ ላይም ያባራ አይመስልም፡፡ የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ በፖለቲካ ሥላቅ ስርአቱ ላይ ርእዮተ ዓለማዊና ሞራላዊ ጥቃት የሰነዘረ ይመስላል፡፡ በመጀመሪያ ቃል ነበር ይላል መጽሀፉ፤ በመሀልም በመጨረሻም ጭምር አለ እላለሁ እኔ፡፡
ወደ መደምደሚያዬ ስመጣ ደራሲው በዚህ መድበል ውስጥ ያሉትን ትረካዎች ለአንባቢ ሲያቀርብ በአብዮቱ ማግስት ከተደረጉት፤ ከተነገሩትና ከተሰሙት እልፍ አእላፍ እውነተኛ ገጠመኞች ተነስቶ ስለሆነ የታሪክ ችግር አልገጠመውም፡፡ በአመዛኙ ተራኪው ሁሉን አወቅ  ሆኖ  በየትረካዎቹ መግቢያና መውጫ ላይ ትዝብት አዘል አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ ዘመኑም ነገሮች የሚለዋወጡበት፤ የሚገለባበጡበት፤ እንደ መብረቅ ብልጭታ ድንገተኛ፤ እንደ ነጎድጓድ ማስገምገም አስበረጋጊ የሚባሉ ፈጣን ድርጊቶች የበዙበት በመሆኑ ምክንያት ይመስላል ሴራው ቀርፋፋ አይደለም፤ ገጸባህሪያቱ ሁለት አይነት ናቸው፡፡ ወይ ወደው ወይ ተገደው እዚያ አዲስና እንግዳ የኅላዌ ሁኔታ ውስጥ የገቡ በመሆናቸው አንድም ባይተዋር አለዚያም ንቁ ናቸው፡፡ ባይተዋርነታቸውም ሆነ ንቁ ተሳታፊነታቸው የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸው ላይ ብዙም ለውጥ ያለው አይመስልም፡፡ በገጸ ባህሪዎቹ የመጨረሻ ዕድል መሰረት ስንመዝነው ድርሰቶቹ አሳዛኝ ሥላቅ (Tragic Satire) ሆነው ይደመደማሉ፡፡ በማጠቃለያ ምን ልንማር እንችላለን? በኔ ግምት ተራኪው “ሁኔታዎች በተቀየሩ መጠን ያው በፊት እንደነበሩት ናቸው” የሚለውን የፈረንሳዮች አባባል በይፋ እንደማይቀበል በግልጽ ቢያሰፍርም (ገጽ 263) በቀል፤ክህደት፣ ክፋት፤ጭካኔ፣ ተስፋ መቁረጥ እና ሰቀቀን በአብዮት ማግስት ሰብሰብ ከማለታቸው በቀር በፊትም የነበሩ በኋላም አሉ፡፡ በሥላቁ ውስጥ ያለው የሥርአት ጉድለትም፤እንከንም፤መንጠራራትም ከቀዳሚው ጊዜ ምንም ለውጥ የለውም፡፡