Wednesday, 11 March 2015 11:18

“ስልት፣ ሂስ እና ሀገር”-

በገብረክርስቶስ ግጥሞች

   “…በቃል ለመግለጽ የሚያቅተኝን በቀለም ቅብ እገልጠዋለሁ፡፡ በሥዕል ለመግለጽ የምቸገርበትን በቃላት /በግጥም/ ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡”      (ገብረክርስቶስ ደስታ)
“በጥበቡ አገር ሙሉ የሆነ፣ አድማሱ የሰፋ ነው፡፡” (ዮናስ አድማሱ)
“…የአማርኛን ስነግጥም አዲስ አቅጣጫ ለማስያዝ ከታተሩትና ከተቻላቸው ገጣሚያን ተርታ የሚመደብ ነው፡፡…” (ብርሀኑ ገበየሁ)

በሀገራችን የስነ ጥበብ ጉዞ ውስጥ የገብረክርስቶስ ደስታን ያህል ከአንድ በላይ በሆኑ ጥበባት “በምልዐት” የተራቀቀ ከያኒ ያለ አይመስለኝም፡፡ ገብረ ክርስቶስ ድንቅ ሠዓሊ፣ ገጣሚና (በእኔ እምነት) ሀያሲም ነው፡፡ “ሰይፍ ዘክልኤ” እንዲሉ፡፡ ለዚህም አዳዲስ ብልሀትን እና ፈለግን እስከማስተዋወቅ ድረስ የተጠበበባቸውን ስራዎቹን (ሥዕሎቹን እና ግጥሞቹን) እንዲሁም በሁለቱ ጥበባት ላይ በየአጋጠሚው የሰነዘራቸውን ብያኔ አከል አስተያየቶቹንና ፍልስፍናዎቹን ልብ ማለቱ በቂ ይመስለኛል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ትኩረት በተለይ የገብረ ክርስቶስን ገጣሚነት ማዕከል አድርጎ ሦስት ነገሮችን መዳሰስ ነው። ቀዳሚው ገብረ ክርስቶስ ለአማርኛ ስነ ግጥም ከስልት እና ብልሀት አንጻር ያበረከታቸውን አስተዋጽዖዎች እየነቀሱ ማሳየት ነው፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ገብረ ክርስቶስ ስለቋንቋና በአጠቃላይ ስለ ስነጽሑፍ የሰነዘራቸውን ሀሳቦች አስረጂ በማድረግ ሰውየው ከገጣሚነቱም ባለፈ ሰፊ የስነጽሑፍ ሂስ ዕውቀት እንደነበረው ማሳየት ነው። ሌላውና የመጨረሻ ጉዳይም በእኔ እምነት በገብረ ክርስቶስ ግጥሞች ውስጥ በጭብጥነት አብዝተው ይከሰታሉ ከምላቸው ጉዳዮች መካከል “ሀገር”ን ጭብጣቸው ያደረጉቱን ግጥሞች  በመውሰድ ትንታኔ ብጤ ማቅረብ ነው፡፡
ይህንንም ሳደርግ እንደተለመደው ሁሉ ከከያኒው ጋር የነበራቸውን ትዝታ የተረኩ ወዳጆቹን ማስታወሻዎች፣ በተለይ ግጥሞቹን ያጠኑ አጥኚዎችን ጽሑፎች፣ እንዲሁም ራሱ ገብረ ክርስቶስ በተለያዩ ወቅቶችና አጋጣሚዎች የተናገራቸውንና የከተባቸውን ሀሳቦች እንደአስፈላጊነቱ እየጠቀስኩ እገለገላለሁ፡፡    
፩. እንግዳ ግጥማዊ “ብልሀቶች”
በ1950ዎቹና 60ዎቹ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ኪነጥበብ ታሪክ ታላቅ ቦታ ካላቸው ጠቢባን መካከል ገብረ ክርስቶስ አንዱ መሆኑን አበክረው የሚገልጹት ብርሃኑ ገበየሁ “…የአማርኛን ስነግጥም አዲስ አቅጣጫ ለማስያዝ ከታተሩትና ከተቻላቸው ገጣሚያን ተርታ የሚመደብ…” መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ገብረ ክርስቶስ ደስታ በሠዓሊነት ከመታወቁ አስቀድሞ ግጥሞችን ይጽፍ እንደነበረ ይነገራል፡፡ ከ1947 ዓ.ም ጀምሮ በወቅቱ በሀገራችን ይታተሙ በነበሩት “አዲስ ዘመን” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ድምጽ” ጋዜጦች, እንዲሁም በ“አዲስ አበባ ስነጥበብ ትምህርት ቤት” ይታተም በነበረ ዓመታዊ መጽሔት ላይ ግጥሞቹን ያሳትም እንደ ነበረ የገብረ ክርስቶስን ግጥሞች በማጥናት ቀዳሚ የሆኑት ስዩም ወልዴ “የሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ግጥሞች” (1981) በተባለው ጥናታቸው ይገልጻሉ፡፡
ሆኖም ይህ ብቻውን “ገብረ ክርስቶስ ቀድሞ ገጣሚ ነው የነበረው፡፡ ሠዓሊነቱ በኋላ ነው የመጣው” አያሰኝም። የዚህም ምክንያቱ አንድም በሥዕል ከመታወቁ ቀድሞ ግጥሞቹን በጋዜጦችና በመጽሔት አሳተመ ማለት ቀድሞ አይስልም ነበር ስለማያሰኝ፤ አንድም ራሱ ገብረ ክርስቶስም ሆነ ሌሎች የሱን “መንታ ጠቢብነት” ያጠኑ ሰዎች የሚሉን ለዚህ ድምዳሜ የማይጋብዝ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሙግት ለጊዜው ትተን (ትኩረታችን አይደለምና) ገጣሚነቱንና ግጥሞቹን ይዘን እንቀጥል፡፡
ገብረ ክርስቶስ በአካል ከዚህ ዓለም እስከሚለይ ድረስ (በ1974 ዓ.ም ነው ያረፈው) በርካታ ግጥሞችን ጽፎአል፡፡ “የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት” (ምስጋና ያንሰዋል) በ1998 ዓ.ም. የከያኒውን ግጥሞች ለመታደግ ባደረገው ጥረት ከያሉበት ሰብስቦ “የህትመት ብርሃን” እንዲያዩ ካደረጋቸው 54 ግጥሞች ሌላ በየሰው እጅ ያሉ ወይም ጭራሹኑ ጠፍተው የቀሩ የከያኒው ግጥሞች እንዳሉ ይታመናል፡፡
ገብረ ክርስቶስ በግጥሞቹ ለአማርኛ ስነግጥም አያሌ ኪናዊ ብልሀቶችን እና ስልቶችን አስተዋውቋል። ይህንንም ሲያደርግ በስልቱ/በብልሀቱ በራሱ አንዳች መልዕክትን ለማስተላለፍ ነው፡፡ ቃላቱ ከሚሰደሩበት ቅጥ የሚነቃ ፍቺ ቢሉ ትርጓሜ አለ፡፡ ይህ የከያኒው ፈለግ የተነደፈባቸው በርካታ ግጥሞች አሉ፡፡
የሚያጽናኑ
ጅምር ሥራ፤
 በየጊዜው የሚያድግ፤
 ቀን የሚገፋ
 ትንሽ ክፍል፤
 ከዓለም ጣጣ የምትከልል፤
ትንሽ ወንበር፤
የምታቅፍ፤
የምትደግፍ፤...
በዚህ ግጥም፣ ግጥሙ የተሰሩበት ቃላት ካዘሉት መልዕክት ባለፈ (ምናልባትም በበለጠ) የግጥሙ መልዕክት የሚሰርጸው ቃላቱ ከተደረደሩበት ቅጥ ይመስለኛል፡፡ የግጥሙ ቃላት በነባሩ መንገድ ወደታች ቁልቁል ተደርድረው ቢጻፉና አሁን በተደረደሩበት መንገድ ሲጻፉ የሚያዘምሩት ፍቺ የተለያየ ነው፡፡ በቀጥታ ከምናገኘው የግጥሙ መልዕክት ባለፈ፣ ከቃላቱ አሰዳደር ቁሳቁሶቹ ቤት ውስጥ እንደምን ባለ መልኩ እንደሚገኙም ጭምር ገጣሚው ይነግረናል፡፡
ፍቅር ጥላ ሲጥል
በገና
ቢቃኙ፤
ሸክላ
ቢያዘፍኑ
ክራር
ቢጫወቱ፤
ለሚወዱት
ምነው…
ቃላቱ ባልተለመደ መልኩ የተደረደሩ ናቸው። በአንድ መስመር ሊቀመጡ የሚችሉት ቃላት ሁለት አንዳንዴም ሦስት እየሆኑ ወደታች በፍጥነት ይጣደፋሉ። ይህ እንዲሁ በዘፈቀደ የሆነ አይደለም፡፡
ከዚህ የነጠላ ቃላት ሰልፍ የሚነቃ መልዕክት ቢሉ ፍቺ አለ፡፡ ከገብረ ክርስቶስ በፊት በአማርኛ ስነጽሑፍ ውስጥ (በዝርውም ሆነ በግጥም) በዚህ “መንገድ” የጻፈ ሰው አላጋጠመኝም፡፡
ከአጠቃላይ የግጥም አጻጻፍ ቅርጽ አንጻር ከያኒው ለአማኛ ስነግጥም ያስተዋወቀውን አዲስ አደራደር እንደምሳሌ አነሳሁ እንጂ የገብረ ክርስቶስ መራቀቅ ከዚህም ያለፈ ነው፡፡ ምናልባትም የዚህ ምክንያቱ ያልተገደበ አንክሮውና ትጋቱ ይመስሉኛል፡፡ ነገሩን በደማቁ እንድንረዳው ጉዳዩን አስመልክተው ብርሃኑ ገበየሁ “ዘመናዊ የአማርኛ ስነግጥም፤ አንዳንድ ነጥቦች” (2001) በተባለው ጥናታቸው ያሉትን ዘለግ አድርጌ ልጥቀስ፡፡
“ገብረ ክርስቶስ ለስፍራና ለቀለም፣ ለአቅጣጫና ለንቅናቄ ታላቅ ትኩረት የሚሰጥ ገጣሚ በመሆኑ፣ በተለይ ወደሁዋለኛው የገጣሚነት ዘመኑ በስንኝ ወርድ እርዝማኔና እጥረት፣ ንቅናቄንና የስሜት ፍላትን…፣ በጽሁፋዊ ምልክት በተለይ በጽሁፍ ውስጥ አገልግሎት ላይ በማይውል ረጅም ሰረዝ ወይም ዳሽ /          / የጊዜን እርዝማኔ፣ ድንገት መጥፋትንና መሰወርን ወይም መክዳትን… እንዲሁም የተቆራረጡ ነጠብጣቦችን /_______/ ለሃሳባዊ ጉዞና ለፍለጋ ወዘተ የሚገለገል፣ ቃል የሚሰንፍበትን ስሜትና ፍቺ በመስመራዊ ምልክትና በአደራደር ለመያዝ የተቻለው ታላቅ ጠቢብ ነው፡፡”
የገብረ ክርስቶስ ግጥሞች የራሳቸው ሙዚቃና ምት ያላቸው ናቸው፡፡ ከያኒው በግጥሞቹ አዳዲስ ስልቶችን/ብልሀቶችን በማስተዋወቅ ግለኛ የሆነ የአሰነኛኘት ፈለግን ቢከተልም፣ የአማርኛ ቋንቋን ውበትና ለዛ ግልጽና ቀላል ሆኖም፣ ቅኔያዊ ውበትን በተጎናጸፈ የገለጻ ኃይል እስከ ባህላዊው ትውፊት ድረስ ዘልቆ መተርጎም የቻለ፣ ግጥሞቹም ህይወትን የሚያንጸባርቁለት ገጣሚ ነው፡፡
ሌላው ምናልባትም በዘመኑ ከነበሩ ገጣሚያን ገብረ ክርስቶስን የሚለየው ነገር ሲጽፍ ቀላል ቋንቋን የሚጠቀም መሆኑ ነው፡፡ በግጥሞቹ ውስጥ የምናገኛቸው ቃላት ቀላልና ግልጽ ናቸው፡፡ በመሆኑም በግጥም ንባብ ወቅት ልንተገብራቸው የሚገቡትን ሌሎች ጉዳዮች (ጥልቅ ንባብ፣ ማሰላሰል.. የመሳሰሉትን) እስከተገበርን ድረስ የገብረ ክርስቶስን ግጥሞች ለመረዳት ግጥሞቹ የተሰሩባቸው ቃላት አይገዳደሩንም፡፡
ከስልት አንጻር ይህንን ያህል የሚራቀቀው ከያኒው በግጥሞቹ በርካታ ጉዳዮችን/ጭብጦችን አውስቷል። በአንዳንዶቹ ጭብጦችም ላይ የጻፋቸው ግጥሞች ከተሰናዱበት ብልሀት ባለፈ የቀረቡበት መንገድ እጅጉን ሳቢ በመሆኑ ልብ ላይ ታትመው የመቅረት ኃይል ያላቸው ናቸው፡፡ በተለይ ስለ ሀገር የተቀኘባቸው ግጥሞቹ እነ “እንደገና”፣ “ሀገሬ”… እንዲሁም የፍቅርና የትዝታ ግጥሞቹ እነ“ትዝታ”፣ “የፍቅር ሰላምታ”፣ “ፍቅር ጥላ ሲጥል”፣ “እኔ እወድሻለሁ”፣ “ከሞተች ቆይቷል”… እጅጉን አይረሴና ልብ ላይ ተንሰራፍተው የሚኖሩ ናቸው፡፡
ዮናስ አድማሱ(ዶ/ር) “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” ለተባለው ብቸኛው የገብረ ክርስቶስ የግጥም መድበል “ያላለቀ መግቢያ” በሚል ርዕስ በጻፉት መግቢያ ላይ ያሰፈሩትን ጠቅሼ ይህን ጉዳይ ላብቃ፡፡ “ግጥሞቹን ብቻ እንኳን ለሚመለከትና በውል ለማጤን ለሚችል፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ሜዳ ሙሉ ጥበብ መሆኑን መረዳት ያስቸግር አይመስለኝም፡፡”  
፪. ገብረ ክርስቶስና ሂስ
በእኔ እምነት ገብረ ክርስቶስ ሠዓሊና ገጣሚ ብቻ አልነበረም፡፡ ምንም እንኳን በዘመኑ ይወጡ በነበሩ ጥበባዊ ስራዎችና በአጠቃላይ በስነጽሑፍ ላይ የተለያዩ “ሂሶችን” ይሰነዝሩ እንደነበሩት እንደ እነ ሰሎሞን ዴሬሳ፣ አቤ ጉበኛ፣ ዳኛቸው ወርቁ(?)… ወዘተ ሂሱን ስራዬ ብሎ ባይዘውም አልፎ አልፎ በየአጋጣሚው ይሰነዝራቸው የነበሩት ስነጽሑፋዊ ሀሳቦች፣ እንዲሁም ግጥሞቹን ለማሳተም ባሰበበት ወቅት ለመድበሉ በጻፈው “ያላለቀ መቅድም” (ጽፎ አልጨረሰውም) ላይ ያነሳቸው ስነጽሑፋዊ ጥልቅ ሀሳቦች… ከያኒው ከመግጠም ባለፈ ሰፊ የስነጽሁፍ ሂስ ዕውቀት እንደነበረው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በመድበሉ መቅድም ላይ ያሰፈራቸውን አንድ ሁለት ሀሳቦች በማንሳት ድምዳሜዬን ላብራራ፡፡
“ዕውነተኛውን ድርጊት፣ ዕውነተኛውን ስሜት ለመግለጽ ቃላት ራሳቸው ደካሞች ናቸው፡፡ አንዳንዴ በቂ ሆነው የማይገኙበት ጊዜ አለ፡፡”
“ቃላት ግጥም ሲሆኑ መምሰል፣ መወከል፣ ትተው ራሱን ሆነው ይገኛሉ፡፡ ይመስጣሉ፡፡ ይሸፍታሉ፡፡ ምትሀት ይሆናሉ፡፡ ሥጋውን ወደ መንፈሳዊ ደረጃ ያደርሳሉ፡፡ ያሻግራሉ፡፡”
ቀዳሚው ገለጻ ገብረ ክርስቶስ የቃላትን የአቅም ውስኑነት የገለጸበት ነው፡፡ ቃላት የሚፈለገውን ሁሉ በምልዐት ለማለት ውስኑነት አለባቸው፡፡ ደካሞች ናቸው። (አንዳንዴም) በቂ አይደሉም፡፡ ታዲያ እንደምን ሆነው ነው ረቂቅ ቢሉ ግዘፍ ሀሳቦችን የሚሸከሙት? አንድም ከቃላቱ ባሻገር የሰው ልጅ ለመግባባት ቅን ፍላጎት ያለው በመሆኑ ከቃላቱ አልፎ ስለሚተረጉም ሲሆን ሌላው ደግሞ አድማጩ/አንባቢው ቃላቱ የተነገሩበትን አውድ፣ ድምፀትና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ስለሚያስገባ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉን ለማለትና ለማስተላለፍ ውስኑነት ያለባቸው ቃላት ግጥምን እንደምን ይሰሩታል? ወይንም ግጥም ውስጥ ሲገኙ ምን ይመስላሉ? ሁለተኛው ገለጻ ለቀዳሚው ምላሽ የሚሰጥ ይመስላል፡፡ ቃላት በግጥም ውስጥ ሲገኙ (“ግጥም ሲሆኑ”) በራሳቸው የነበረባቸውን ውስኑነት ተላቀው ምልዑ ይሆናሉ፡፡ ምልዐታቸውም ያህላል የማይሉት ነው፡፡ መምሰልን እና መወከልን ትተው ራሳቸው ሀሳብ ይሆናሉ፡፡ ይልቁንም ወደ መንፈሳዊ ደረጃ ያሻግራሉ፡፡ ማለትም ከሥጋ ይልቅ ለነፍስ፣ ከጆሮ ይልቅ ለልብና ለአእምሮ ይሰማሉ፡፡ የቃላትን ተፈጥሮአዊ ባህሪና ግጥም ውስጥ ሲገኙ የሚኖራቸውን ህልውና እንዲሁም አገልግሎት አስመልክቶ ገብረ ክርስቶስ የሰነዘራቸው ሀሳቦች ብዙ የሚነግሩ እጅጉን ጥልቅና ተጠየቃዊ ናቸው። ግጥምን እና ዝርው ጽሑፍን በማነጻጸር የከተበውን እንጨምር፡፡
“ቅኔ እንደነጠላ ጽሑፍ በዘርፍና በወሬ የተበተበ ሳይሆን የተለቀመና የተጨመቀ ነው፡፡ በግጥም፣ ቃላት ለትርጉማቸው ብቻ ሳይሆን ለውበታቸውም ጭምር ይፈለጋሉ፡፡”
ያሰመርኩባቸው ቃላት ያዘሉት ሀሳብ ላይ ላተኩር። “ቅኔ… የተለቀመና የተጨመቀ ነው፡፡” መለቀምና መጨመቁም ከቃላትና ሀሳቦች ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ቃላትን አይፈልግም ማለት ሳይሆን ይመርጣል፤ ይቆጥባል ማለት ነው፡፡ ሀሳብን አይዝም ማለት ሳይሆን ሀሳብን ይመርጣል፤ ያምቃል ማለት ነው፡፡
“በግጥም፣ ቃላት ለትርጉማቸው ብቻ ሳይሆን ለውበታቸውም ጭምር ይፈለጋሉ፡፡” ይህም ሀሳብ የከያኒውን እውነታ የሚታገግ ይመስላል፡፡ ቃላት በግጥም ውስጥ ሲገኙ በሌሎች የስነጽሑፍ ቅርጾች/ዘርፎች ውስጥ ሲገኙ ከሚኖራቸው ያለፈ አገልግሎት አላቸው፡፡ በተለየ ውበትን የመፍጠር/የመስራት አገልግሎት! የግጥም ውበታት የሚነቁት አንድም ከቃላቱ ነው፡፡ ለምቱ ብንል ለዜማው፣ ለሙዚቃዊነቱም ጭምር የቃላቱ ሚና ታላቅ ነው፡፡
አስረጂ ለማምጣት ያህል እነዚህን አነሳሁ እንጂ የገብረ ክርስቶስን የስነጽሑፍ ሂስ እውቀትና ለዘርፉም የነበረውን ትጋት ግጥሞቹ በራሳቸው የሚያስረግጡ ናቸው፡፡ የተሰናዱበት መንገድ በራሱ ብዙ ይናገራል። ተማሪዎቹና ወዳጆቹ እንደሚሉት ሥዕልን በሚያስተምርበት ጊዜ ይከተለው የነበረው መንገድ (ክሂሉን በቀጥታ ከማስተማር ባለፈ አንድ የጥበብ ስራ ላይ ቆም ብሎ የማሰላሰል፣ የመተቸትና የመተርጎም) በራሱ ገብረ ክርስቶስ ለሂስ የነበረውን ክብር፣ ፍላጎትና ትጋት የሚያሳይ ነው፡፡
፫. “ሀገር” በገብረ ክርስቶስ ግጥሞች
በእኔ እምነት ገብረ ክርስቶስ ግጥምን አብዝቶ ከጻፈባቸው ጭብጦች መካከል አንዱ “ሀገር” ነው፡፡ የሀገር- ትዝታ፣ ባህል፣ እምነትና አስተሳሰብ፣ ወቅቶችና መልክአ ምድሩ… ዙሪያ ገባው በገብረ ክርስቶስ ግጥሞች ተወስቷል፡፡ በወቅቱ በገጠሙት የተለያዩ ምክንያቶች “ተገዶ” የሚወዳት ሀገሩን ጥሎ እስከ ህይወቱ ፍጻሜ ድረስ በባዕዳን ሀገር በስደት የኖረው ገብረ ክርስቶስ በስንኞቹ ስለሀገሩ ብዙ ተቀኝቷል፤ አብሰልስሎአልም፡፡ የገብረ ክርስቶስ ስለ ሀገር መገደድ የበዛ ነው፡፡ ጭብጣቸው ሌላ ጉዳይ በሆኑ አንዳንድ ግጥሞቹም ሳይቀር ሀገርና ጓዞቹን ያቀፉ በርካታ ስንኞችን እናገኛለን፡፡ እነሱን ለጊዜው ትተን አቢይ ጭብጣቸው “ሀገር” ነው ካልኳቸው የከያኒው ግጥሞች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ እያነሳሳሁ ልቀጥል፡፡
የመንደር ጭስ ማታ - -  - -  - -  
ይናፍቀኝ ነበር የሣር ቤት ጥቀርሻው
መደቡ ምሰሶው፤
ማገሩ ግድግዳው፤ አጥሩና ጥሻው፡፡
        የፈራረሰ ካብ - -  - -    
ቀጭን ጠባብ መንገድ በመንደር የሚሮጥ
ቅጠል የሸፈነው፤
                ሣር ያለባበሰው፤
እነዚህ፤ እነዚህ፤ ይናፍቁኝ ነበር፡፡… (“እንደገና”)
ግጥሙ እጅጉን ገላጭ ነው- የገጠሩን ዙሪያ ገባ በምልዐት የሚያሳይ፡፡ እያንዳንዱን የግጥሙን መስመር ባነበብን ቁጥር የምናየው ደማቅ ምስል አለ፡፡ ከጎጆው ቤት አናት ላይ ጢሱ ወደሰማይ ሲጎን፣ የገጠሩ ጎጆ ከእነጓዙ፣ አጥርን ታኮ የሚዘልቅ እግር የበዛበት ቀጭን መንገድ…. ሌላም ብዙ፡፡ ገብረ ክርስቶስ በግጥሙ ከሀገሩ ርቆ ሳለ ሀገሩና ልጅነቱን ያሳለፈበት የገጠሩ መንደር ምን ያህል እንደናፈቀችው ከትቧል፡፡ የከያኒው የሀገር ናፍቆትና ስለሀገር ማንጎራጎር ከዚህም አልፎ ይሄዳል፡፡ የሀገሩ ማዕከል የሆነውን የሀገሩንም ሰው ይናፍቃል፡፡
… ያገሬ ሰው ነበር እኔን የናፈቀኝ፤
ጠይም ቆዳ ነበር እኔን የናፈቀኝ፤
ቀይ ዳማ ነበረ ጥቁር ቆዳ ነበር፤
ቁርንጫጭ ከርዳዳ፤ ዞማ ጠጉር ነበር፡፡… (“እንደገና”)
ስለ ሀገር የሚያወሱት የከያኒው ግጥሞች ትኩረታቸው ብዙ ነው፡፡ ከሀገሩ የራቀ ሀገሩን መናፈቁ፣ በመራቁም ስላጣው ማንጎራጎሩ ልማድ ቢሆንም የገብረ ክርስቶስ ስንኞች ግን ደረቅ ማንጎራጎር አይደሉም፡፡ ውበትና ፍቺን ያጋቱ ቅኔ ናቸው፡፡
…ዐደይ አበባ ነህ የመስቀል ደመራ፤
ጠረንህ አልባብ ነው አየርህ የጠራ፡፡
ያገር ልብስ አንተ ነህ ነጭ እንደ በረዶ፤
ሰው የሚያጌጥብህ ጥበብህን ወስዶ፡፡
ቡቃያ ነህ እሸት ጓሚያ የበሰለ፤
አረንጓዴ ልብስህ በጌጥ የተሳለ፡፡
ጥቁር አረንጓዴ፤ ብጫማ አረንጓዴ፤
ያተር አረንጓዴ፤ ንጹሕ አረንጓዴ፡፡
ቀለም¡ ቀለም¡ ቀለም¡
           የሚስተካከልህ የሚያስንቅህ የለም፡፡… (አንተ ነህ መስከረም)
ግጥሙ የመስከረምን ፍካትና አዲስ ምዕራፍነት ከመግለጽ ባለፈ በሚጠራቸው ልዩ ልዩ ቀለማት (ነጭ፣ አረንጓዴ፣ ጥቁር አረንጓዴ፣ ብጫማ  አረንጓዴ፣ ያተር አረንጓዴ፣ ንጹሕ አረንጓዴ) እንዲሁም ትምህርተ ስላቅን (¡) እያስከተለ ሶስት ጊዜ በሚጠራው “ቀለም” በሚለው ቃል የቋጠረው ፍቺ ስለመስከረም ከማተት አልፎ የሚተረጎም ነው፡፡
በእኔ እምነት ገብረ ክርስቶስ ሀገርን (“ሀገሩን”) ጉዳይ አድርጎ ከጻፋቸው ግጥሞች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚወስደው (በሚያነሳው ሀሳብ ምልዐትና በአሰነዳደቱም ጭምር) “ሀገሬ” የተባለው ግጥሙ ነው። በግጥሙ የኢትዮጵያ “ምንትነት” ያህላል በማይሉት ምልዐትና ውበት ቀርቧል፡፡ ግጥሙ ሀገር ምንድን ናት? ከሚለው ጥቅል ጥያቄ መለስ ብሎ ኢትዮጵያ ምንድን ናት? ለሚል ጥያቄ ውሃ የሚቋጥር መልስ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ጥቂት ስለእሱ ብዬ ሀሳቤን ልቋጭ፡፡
… አገሬ ዓርማ ነው የነጻነት ዋንጭ
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ብጫ፡፡
እሾህ ነው አገሬ፣
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ
ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ፡፡
አገሬ ታቦት ነው መቅደስ የሃይማኖት
ዘመን የፈተነው በጠበል በጸሎት፡፡
ለምለም ነው አገሬ፡፡
ውበት ነው አገሬ፣
ገነት ነው አገሬ፡፡
ብሞት እሔዳለሁ ከመሬት ብገባ
እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ፡፡
ስሳብ እሔዳለሁ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ፡፡
አለብኝ ቀጠሮ
ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ፡፡ (“ሀገሬ”)
የኢትዮጵያ መልክአ ምድር ቢሉ ታሪክ፣ ጀግንነት ቢሉ ነጻነትና አለመደፈር፣ ባህል እምነቱ ከእነጓዙ በግጥሙ ተቀንብቦአል፡፡ ሊያውም በውብና ማራኪ ቃላት! ገብረ ክርስቶስ ይህን ግጥም የጻፈው በጀርመን (ኮሎኝ) ሀገር በስደት ላይ ሆኖ ነው፡፡ በስደት ላይ ያለ ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሀገሩን ያስታውሳል፤ ይናፍቃል፡፡ የትውልድ ሀገሩን ህዝብና ባህል ካለበት ህዝብ አመለካከትና ባህል ጋር ያወዳድራል፡፡ አወዳድሮም የሚደርስበት ውጤት አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ይሰማዋል። ያኔ በሀገሩ ሳለ ልብ ያላለውን ሁሉ ልብ ይላል፤ ዋጋ ላልሰጠው ነገር ዋጋ ይሰጣል፡፡ እናም መሰጠቱና አቅሙ በፈቀደው ልክ ሀገሩን መበየን ይጀምራል፡፡ በዚህ ረገድ የገብረ ክርስቶስ “ሀገሬ” እጅጉን የተዋጣለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ምንድን ናት? ለሚል ጥያቄ ውሃ የሚቋጥር መልስ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ማለቴ፡፡


Published in ጥበብ
Wednesday, 11 March 2015 11:14

አድማስና እኛ

    አዲስ አድማስ ጥንስሱ የተጠነሰሰው፣ በተሟሸና በታጠነ ጋን ነው! ከፕሬስ ህጉ ጋር በተያያዘ የተነሱትን ጋዜጦች አስተውለን፣ የአንባውን አቅምና የወቅቱን አየር አጢነን፣ የሀገራችንን የዕድገት ደረጃ መዝነን፣ አዕምሮአችንን በወጉ አትብተን ስለተነሳን ነው በተሟሸ በታጠነ ጋን ነው የጠነሰስነው የምንለው!
መረጃ መስጠትና ማዝናናት ዋና ዓላማችን ነው Infotainment! ለምን? መረጃ አጥቷል ወይ ህዝቡ? አዎን አጥቷል! የሚያዝናናውስ ነገር አጥቷል ወይ? አዎ ነው መልሱ፡፡ መዝናኛው ግን መገለጢጥ (Unseasoned‚ untrimmed) መሆን የለበትም፣ አልን፡፡
እኔና አሰፋ ጎዳዬ (አሴ) ቀደም ብለን ብንተዋወቅም፣ በሥራ መንፈስ አልተሳሰብንም ነበር፡፡ ልብ ለልብ መግባባታችንን ግን በቅጡ አውቀናል፡፡ ከአንድ ኢ.ሲ.ኤ (ECA) ካለ ወዳጄ ጋር በተመካከርነው ሀሳብ መነሻነት አንድ የኮሙኒኬሽን የሽርካ ኩባንያ (Share Holders Company) ልናቋቁም አቅደን ሁላችንም ወደምናውቃቸው ወዳጆች እንሂድና አባላት እናሰባስብ ተባባልን፡፡ በዚህ መሰረት እኔ ከቅርብ ወዳጆቼ መካከል ወደ ሆነው ወደ አሰፋ ጎሳዬ ሄድኩኝ፡፡ ሀሳቡን ወዶታል፡፡ ግን እሱ በልቡ የያዘው ጉዳይ አለው፡፡
“የአክሲዮኑ አባል ለመሆንና ገንዘብ ለማዋጣት እችላለሁ፡፡ ያ ግን ውስጤ ያለውን ሀሳብ እንደማያዳክመው ተስፋ አደርጋለሁ” አለኝ፡፡
“ምንድን ነው ሀሳብህ? በግልፅ ንገረኝ?” አልኩት፡፡
“አንድ ጋዜጣ መፍጠር አለብን”
“ምን አይነት?”
“ለአንተ የሚመችህን ዓይነት”
“እንደዛ ከሆነ እኔ የማስበውን ልንገርህ” አልኩት፡፡ “Cultural revolution lags behind. Politics is the concentrated form of economics” የሚለውን ማርክሳዊ አካሄድ በኢትዮጵያ መንፈስ ሳስበው ገና ያላጸደቅነው፣ ያልሰለቅነው ብርቱ ሀሳብ ያለ ይመስለኛል፡፡ እንደ ሀገራችን ሁኔታና የዕድገት ደረጃ ከሆነ ለእኔ ዋናው ቁምነገር ባህል ነው - ቀዳሚ ነው! ባህላዊ ግንዛቤያችን በቅጡ ካልተውጠነጠነ ማናቸውንም ዓይነት ፖለቲካ ብንጭንበት ባዕድነቱ አይቀሬ ነው፡፡ በቀላሉ አይዋሃደንም፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ አንፃር ከነአካቴው ዘይትና ውሃ ይሆናል፡፡ ባህልን ጉዳዬ ብለን ብናሰላ፡- አንደኛ/ የራሳችንን ስነልቦና የምናወጣበት መላ እናገኛለን፡፡ ሁለተኛ/ ባህላዊ እሴቶቻችንን ማሳያና ማጎልበቻ መላ እንፈጥራለን፡፡ ሶስተኛ/ በባህላዊ መንገድ የልባችን የምንለውን ፖለቲካዊ ጉዞ እንዳስሳለን፡፡ የራሳችንን ታላላቅ ሰዎች እናሳውቃለን፡፡ Guided democracy (መሪ የፈቀደው ዓይነት ዲሞክራሲ)ም ሆነ Tailored democracy (በልካችሁ እንስፋላችሁ የሚባል ዲሞክራሲ) እንደማይጠቅመን ማስረጃ እናቀርባለን፡፡ ውለን አድረንም የራሳችንን ልበ - ሙሉ ዲሞክራሲ (Full – fledged and focused to our advantage) የሚያሳይ ጋዜጣ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ሀሳብ ማንሸራሸሪያ መድረክ እንፈጥራለን” አልኩት፡፡
“ዕውነት ነው፡፡ ማንም ሀሳቡን የሚያሰፍርበት ጋዜጣ ነው መሆን ያለበት!” አለኝ፡፡
“አዎ ግራም ይሁን ቀኝም የእኔ ነው ብሎ አምኖ ህዝቡ ፅሁፉን መላክ አለበት፡፡ የእኔ ነው ብሎ ማመንም አለበት”
“ስለዚህ ‹የእርሶና የቤተሰብዎ ጋዜጣ› ብለን ማስረዳት አለብን” አለኝ አሴ፡፡
“ምንም ወደኋላ የማልልበት ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ያሉትን ጋዜጦች ግን ባህሪያቸውን ማወቅና የእኛን ጋዜጣ አካሄድ ማስተዋል ይገባናል”
“አንተ እንዴት ታያቸዋለህ?” አለኝ መልሶ፡፡
“አየህ ባሁኑ ጊዜ፤ በሁሉም ረገድ ፅንፍ ብቻ ነው ያለው፡፡ ወይ ነጭ ነው፡፡ ወይ ጥቁር ነው፡፡ እንጂ መካከል ላይ ላለው ህዝብ አልታሰበለትም፡፡ እንደ ሀገራችን ዕሙናዊ ዕውነታ ካየን፣ ከጥንቶቹ ፖለቲከኞች ማለትም ወይ ነጭ ወይ ጥቁር ይልቅ ግራጫው ክፍል (ፖለቲካ አይሻኝም አርፌ ስራዬን ልስራ የሚለው) ይበረክታል፡፡ ይሄንን ክፍል እንዴት እንድረሰው? ምን ዓይነት ጽሁፍ እናቅርብለት?”
አሴ ጉድ ያመጣው ይሄኔ ነው!
“ነቢይ” አለ “አየህ እኔ የጋዜጣ ህልም ያደረብኝ ዛሬ አይደለም፡፡ ድሮ ነው በጣም ድሮ! ደሞ ልብ አለኝ! እሰራዋለሁ!”
ዛሬ ሳስበው የዚያን ጊዜውን አሴ የሚከተለው ግጥሜ ይገልፀው ይመስለኛል፡-
 ነገን ትላንትና ያየ
ዐይን ያለው ሰው የት ይገኛል፣ ነገን ትላንትና ያየ፤
ከወዲሁ ራዕይ ያለው፣ መጪ ክፉ ደግ የለየ?
ቅጠልስ ሳይወድቅ ዕጣውን፣ የሚያውቅ አንጎል የቱ ይሆን?
ችግኝስ ሳይኮተኮት፣ ማደግና አለማደጉን -
ማወቅ የሚችል ማን ይሆን?
አገርስ ታምማ ስትተኛ፣ አሊያም ድና ስትነሳ
ማነው ትንቢቷ እሚገባው፣
ማነው ተረዳሁ እሚለው?
ረብ ያለው ትውልድ ማብቀሏን፣ እናታችን ፍም አውርሳ
በምጧ ልታሳድገን፣ ታርሳ ተምሳ ተክሳ፣
አህያ ወልዳ ማረፏን፣ በለሆሳስ ልታወሳ?!
የተረዳ ሰው ማነው?
አንዳንድ ጥበብ መነሻው፣ ማወቅን አለመፍራት ነው
አንዳንድ ጥበብ መሞቻው፣
አለማወቅን መድፈር ነው!
ማወቅና አለማወቅ፣ ዞሮ ገጠም ቀለበት ነው፤
በማወቅ ውስጥ አለማወቅ
ባለማወቅም ውስጥ ማወቅ
መኖሩን የምናጤነው፣ ድንቁርና ላይ ስንስቅ
ነውና ከዕንባችን ቀድመን፣ የሳቅን እሳት እንሙቅ!!
ያኔ ነው አገራችንን፣ የነገ መልኳን የምና‘ቅ!!
የካቲት 24 2007 ዓ.ም
አሴ ከዚህ በኋላ ነው ገና ጋዜጣው ሳይጀመር ከባሴ ሀብቴ ፅሁፍ ሲገዛ እንደነበር የነገረኝ፡፡ አልፎ ተርፎ የእንግሊዘኛ መጽሔት እየሰጠ ያስተረጉመው እንደነበረም አወኩኝ፡፡ ከእኔም ከዕለታት አንድ ቀን የገዛቸውን ጽሑፎች ለጋዜጣው እንደሚያውል ሚሥጥሩን ሹክ ያለኝ ይሄኔ ነው፡፡ አርቆ ማሰቡ ደስ አለኝ፡፡ አሰፋ ማለት ይሄ ነው!
ከጌታ መኰንን፣ ከበቀለ መኰንን፣ ከተፈሪ ዓለሙ፣ ከሰዓሊ መስፍን …ጋር ሆኖ Addis Art Week የሚባል ህፃናትን መንገድ ላይ ስዕል እንዲሰሩ የሚያደርግ ፕሮግራም ማቀዱን ሳውቅ ደግሞ የባሰውን ኢኮኖሚስቱ (ጉራጌው) አሰፋ፤ ጥበብ የገባው መሆኑን አየሁ፡፡ ይህ ሰው እንደሚገባኝ እሱንም እንደምገባው ያለጥርጥር አውቄያለሁ፡፡ ስለዚህ ጋዜጣ እናዘጋጅ ሲል ግርታ አልነበረብኝም፡፡ ከተለያዩ የቲ-ሩም ቆይታዎችና ብሔራዊ አካባቢ ካለው የአድማስ አድቨርታይዚንግ ቢሮ ፊት ለፊት ዘለዓለም ሬስቶራንት (በተለምዶ እንዳለ ቤት የምንለው ነው) ቆይታ በኋላ፤ ኦርማጋራዥ አጠገብ ወደ አሮጌው ቄራ ሲወጣ በስተግራ፤ የሚገኘው ሙሉጌታ ከበደ ኳስ ተጫዋቹ ቢራ ቤት ከፍቶበት የነበረ ቤት ውስጥ ነበረ የአዲስ አድማስ የመጀመሪያ ቢሮ የተከፈተው፡፡ ከአሴ ጋር እዚህም ጽሑፍ ማከማቸት (Back – log ማዘጋጀት የምንለው) ነበር ሥራችን፡፡
ማርቆስ ረታ፣ ብርሃኑ ንጉሤ፣ ተፈሪ መኰንን፣ ሰለሞን ገ/እግዚአብሔር፣ ሰለሞን ካሣ፣ አበበች ካሣ እና ከአዋሳ የመጣችው ፀሐፊያችን የውብዳር በቀለ ናቸው የሥራ ባልደረቦቻችን፡፡ እንዲያው ለወጉ የሥራ ባልደረባዎች እንባባላለን እንጂ ባልንጀራሞች ነን ብል ይቀላል፡፡ እኛ አርቲክል (ሐተታ) ስንፅፍ እንቆይና በሁለት ሶስት ቀን ውስጥ አሴ ይመጣና Where is my beef? ይለናል፡፡ ምሴን ስጡኝ! ምን አዘጋጃችሁልኝ፤ እጃችሁ ከምን? ማለቱ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ ያፋጥጠናል! ግን እየተግባባን እንደሆነ በበኩሌ ጥርጥር አልነበረኝም! ሌሎቹ ከእኔና ከአሴ በዕድሜ ያንሳሉ - ምናልባትም በፖለቲካ ልምድ! በእኔና በአሴ ዕምነት ነጭና ጥቁር ትተን ግራጫውን ንፍቀ ክበብ እንሸፍን የሚለው ሃሳብ ኒሻን ጋዜጣና ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ሲፅፉ ለነበሩት ለባልንጀራ ጋዜጠኞች ግር ማለቱ አይቀሬ ነበር - ዞሮ ዞሮ ግን የጋዜጦቹን አምዶች ስንከፋፈል ሁሉም የየፊናቸውን እንደማያጡ እኔ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
ጋዜጣችን፤ የፊት ገፁ የዜና፣ ሁለተኛ ገጽ - የት እንሂድ፣ ሦስተኛ ገፅ የሰሞኑ አጀንዳ፣ አራተኛ ገፅ - ርዕሰ አንቀፅና መልዕክቶቻችሁ፣ አምስተኛ ገፅ - ነፃ አስተያየት፣ ስድስተኛ ገፅ - ምን ይሻላል? (ሳይኮሎጂ) ሰባተኛ ገፅ - ባህል፣ ስምንተኛ - ሥራ፣ ዘጠነኛ - ትምህርት፣ አሥረኛ - ንግድና ኢኮኖሚ፣ አሥራ አንደኛ - ሳይንስና ቴክኖሎጂ፡፡ አሥራ ሁለተኛው - ዋናው ጤና፣ አሥራ ሶስት - ጥበብ ገፅ፣ ሃያ - ስፖርት አድማስ፡፡ ከእነዚህ አምዶች ብዛት የምንረዳው ምን ያህል ለጋሥ አምዶችን ይዘን እንደተነሳን ሲሆን፤ ለመስሪያቤታችን ብረት መዝጊያ ናቸው ከምንላቸው ቋሚ ሰራተኞቻችን ሌላ፤ እንደ ባሴ ሀብቴ፣ አዶኒስ፣ ስብሃት ገ/አግዚአብሔር፣ ኤፍሬም እንዳለ፣ ተሾመ ገ/ሥላሴ፣ ደራሲ መስፍን ሀ/ማርያም፣ አብደላ ዕዝራ፣ ሰአቸ፣ ጌታቸው አበራ፣ ዶ/ር ሱራፌል ከበደ፣ አልአዛር ኬ፣ ዮሐንስ ሰ.፣ አብዱልመሊክ፣ አሰፋ ጫቦ፣ ሰለሞን በቀለ (ስፖርት)፣ በቀለ መኰንን፣ አየለ እሸቱ፣ እንዳለጌታ ከበደ፣ በዕውቀቱ ስዩም፣ መሀመድ ኢድሪስ፣ ህሊና ተፈራ፣ እቱ ገረመው፣ እዝራ እጅጉ፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ ብርሃኑ ገበየሁ፣ ዳዊት ፀጋዬ፣ ዳደ ደስታ፣ ከበደች ተ/አብ፣ አሸናፊ ዘደቡብ፣ ዳንኤል በላቸው፣ ላምሮት፣ ገነት ግርማ፣ ዶ/ር ሚካኤል ታምሩ፣ ዶ/ር የሺጥላ…ፀዳለ-ጥበብ…ከበደ ደበሌ፣ ቢልቄሣ፣ ሰለሞን ዋሲሁን፣ እመቤት አብዲሣ ወዘተ…ያሉ ድንቅ ፀሐፊዎች ነበሩ ጽሑፍ የሚያዋጡልን፡፡ እኛን እኛ ያደረጉን እኒህ ሁሉ ነበሩ፡፡ በብርቱው እናመሰግናቸዋለን፡፡
ሴንትራ ሸዋ ሆቴል ፊት ለፊት ባለው ቢሮአችን ነበር የጋዜጣ ህትመት ሥራን ሀ ብለን የጀመርነው፡፡ ርኩቻውን፣ ግድፈቱን፣ ማምሸቱን፣ ማንጋቱን ከሞላ ጐደል ሠራተኛው ሁሉ ተጋርቷል፡፡ በአሴ በኩል የምናውቃቸው ጓደኞች ሳይቀሩ አብረውን አምጠዋል፡፡ እጅግ እናመሰግናቸዋል፡፡ እንደ ሰዓሊና ገጣሚ መስፍን ሀብተማርያም ያሉትን የአዕምሮ ሀብቶች መዘንጋት አይቻልም፡፡ እንደ አብርሃም ረታ (ዲቸራ ቀንዶ) ያሉትን ባለሰፊ ምናብ ፀሐፊ ምኔም መርሳት አይቻልም፡፡
አዲስ አድማስ አዲስ ጠላ ለመጥመቅ የተሰባሰቡ አዕምሮዎች ውጤት ነው፡፡ ባህላዊና ጥበባዊ እሴቶችን ለማበልፀግ የተጣረበት ነው፡፡ ወጣት ገጣሚያንን ለማብቃት የአዕምሮ ቀለም አፍስሰናል፡፡ አንድም በመረጃ አቅርቦት፣ አንድም በማዝናናት ብፅዓት፣ የማንበብ ባህል እንዲያድግ የበኩላችንን አዋጥተናል፡፡ የእኛ ጋዜጣ የመቻቻል መናኸሪያ ነው፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው ሥነጽሑፍ የመሆን ትጋታችን የተሳካ ይመስለናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን አሁንም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጋዜጣ ነውና ፀሐፊዎች ናቸው ጉልበታችን፡፡ አንባቢያችን ነው ኃይላችን! የአዲስ አድማስ ዓላማ ዛሬም ኢንፎቴይመንት ነው! እንደሁልጊዜው፤ ስላነበባችሁን ከልብ እናመሰግናለን!!

Published in ጥበብ
Wednesday, 11 March 2015 11:12

አልቀርም መንኩሼ

(የአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት የግጥም ውድድር አሸናፊ)

አልቀርም መንኩሼ
ከዝምታሽ ገዳም
ጠርተሽኝ - ምናኔ፣
እንቢ ብዬ እንዳልቀር
ፈርቼ ኩነኔ፡፡
ብመጣም ዝምታ
ድርብ ተሸምኖ፣
ከገላሽ ላይ ውሏል
ካባ ጃኖሽ ሆኖ፡፡
መች አሰብኩ ለሆዴ
ብኖር ከገዳሙ፣
ሥራስሩን ምሰው
ፍሬ እየለቀሙ፣
ጥራጥሬ ቆልተው
… እየቆረጠሙ፣
ሰርክ እየማለዱ
በፀሎት በፆሙ፣
ሥጋን ወዲህ ጥለው
ነፍስን እያከሙ፡፡
መች ጠላሁ ለመኖር
ፅድቅን እያሰቡ፣
መንፈስ የሚያሸፍት
ሆነ እንጂ ድባቡ፡፡
ከዝምታሽ ገዳም
ዝምታሽ ጨምቶ፣
እርቃኑን ካልቀረ
ካባ-ጃኖ ትቶ፡፡
በሳቅ ካላፈካው
ድባቡን ለውጦ፤
ዝምታሽ ካልዋጠው
ዝምታን አላምጦ፡፡
ልውረድ ከመቀመቅ
ያብቃኝ ለኩነኔ፣
መንኩሶ ከመቅረት
ይሻለኛል ለኔ፡፡  

Published in ጥበብ

አዲስ አድማስ ጋዜጣ ለአስራ አምስት አመታት ጨለማና ብርሃን እየሰነጠቀ ለመነበብ መብቃቱ የዋዛ እድሜ አይደለም። ልደታችንን ስናከብር ዳቦ በመቁረስና ወደፊት በመገስገስ ብቻ መቀንበብ አይመጥነንም፤ በፈጠራ ድርሰት ሶስት ምርጦችን መሸለምና ማበረታት ለጥበባዊ ተስፋም አስተዋፅዖ ነው። በግጥምና አጭር ልቦለድ የተሳተፉትን ሁሉ እናመሰግናለን። በሥነፅሁፍ እንቅስቃሴ የሆነ ደራሲ-ገጣሚ የተለመደውን ድንበር በመሻገር ብርቅ ጽሑፍ ለማጣጣም ይፈቅድልናል ብለን ብንጓጓ እንኳን፥ በውድድሩ ለመሳተፍ በማቅማማቱ ሳቢያ ተነጥቀናል --አይኖርም አትኖርም ብለን አንደመድምም። በአንፃሩ ግን ሲነበቡ የማይሰለቹ፥ ህይወትን አዛዙረን ምስጢሩን ለመቅሰም ያነቃቁን በግጥምም በአጭር ልቦለድም ሶስት ብዕሮች አሸናፊ ሆነዋል። ስድሳ ግጥሞች እና አርባ አራት አጫጭር ልቦለዶች ከምናባችንና ጥሞናችን ፈክተውም ተስለምልመውም ሶስቱ አጐንቁለው ፀደቁ።

የአጭር ልቦለድ ውጤት
አንደኛ    የትዕግስት ተፈራ “ፀሐይ” ፤ ከደረት ፈልቃ ሣቅ መስላ የከበደች ጩኸት እያስታመመ በእናቱ ሞት ውስጡ የተመዘመዘ ግለሰብ፥ ጋቢ   ደርቦ ለቀናት ባለመቆዘሙ ማኅበረሰቡ ተንሾካሾከበት። ደራሲዋ ድርጊትንና ሥነልቦናዊ ውስጠትን በመበርበር የእናትና የተፈጥሮ ፀሐይን ቅኔያዊነት በመገንዘብ ሳታንዛዛ፥ የጐርፍን ተምሣሌት እስከ ምትሀታዊ እውነታ -magic realism- ተሻገረችበት፤ ትረካዋ ይመስጣል።
    አለመደማመጥ ሰውን ከእብደት ጠርዝ ሊያንፏቅቀው መቻሉ ያሳስበናል፤ የሌላው መታወክ ቀርቶ፥ የእጆቹ መንቀጥቀጥ እንኳን በቂ ምልክት ነው፤ የግለሰብን ሥነልቦናዊ መድፍረስ ለማጤን።
ሁለተኛ    የፍፁም ገ/እግዚአብሔር “የዱበርቲዋ ጀበና”፤ በጉጉት የሚነበብ ብቻ ሳይሆን በቀበልኛ ቋንቋ የወረዛም ልቦለድ ነው። “ፍርሀት ሆድ ውስጥ ገብቶ፥ እንደ ቅቤ መግፍያ ቅል መናጡ” ያልገታው ገፀባህሪ፥ ደም እንዳይቃባ ለመካስ ጥማድ በሬውን የሸጠ ግለሰብ ይከታተላል። ለአድባር ቡና አፍልተው፥ ለሴት ዛራቸው የሚስጉት ዱበርታዊ ትረካውን ያበለፅጉታል። የኑሮ አጋጣሚ ሲያደናቅፍ ለፈጣሪ ከማደር በላቀ ለተውሳከ-እምነት መሸነፍ ከጀበና ዋልታ ዙሪያ ተጠንጥኖ መንደሩ ይታመሳል።
ሶስተኛ    የሀውኒ ደበበ “በሩን ክፈቱልኝ”፤ የመንፈስ መታወክና ስጋት ከልቦናዋ ሰርገው ለመተንፈስ የሚከፈት በር ፍለጋ አንዲት ወጣት ታቃስታለች። በሶስት ጐረምሶች በአስራ ስድስት አመቷ የተደፈረች ልጃገረድ ለአመታት ተንገላታለች። ለትልሙ -plot- ቆምታ የስሜት ይሁን የቁሳቁስ ርዕስ እየተሾመ (እንባ፥ ዛሬ፥ ሙሽራ ቀሚስ ...) ሣይበተን የሚሰበሰብ ልቦለድ እንደ ግለታሪክ ወይም የእለት መዝገብ ይነበባል። ከመደፈር የባሰ ሰቆቃው እውስጣችን ዘቅጦ የሚታመሰው ዕዳ መሆኑን በማጤን ደራሲዋ እስከ መንፋሳዊ ጓዳ ዘልቃበታለች።

የግጥም ውጤት
አንደኛ    የየማነ ብርሃኑ “አልቀርም መንኩሼ”፤ ዝምታን አላምጣ ተናጋሪውን ያገለለች እንስት ትሁን ተምሣሌት ያማሰለችው ህላዌ አልሰከነም። ቋንቋና ዘይቤው ጥልቀት ለግሰውት እስከ መንፈስ ዳርቻ ለመዝለቅ ስንኞች አልሰነፉም። ወንጌላዊ ቃና ለምድር ፍላጐት ፈረጠበት።
ሁለተኛ     የደመረ ብርሃኑ “ሞልተዋል ብላቴና”፤ ሰሌዳ ዕውቀት የሚፈካበት የተወጠረ ዝርግነት ሳይሆን፥ በማድያት ተላልጦ መማርና መብሰል ይፋቁበታል። በሚነዝር ቋንቋ እየኮሰኮሰን፥ላልጠና አእምሮ ገጣሚው ተብሰክስኳል። የግል ቁዘማ ሳይሆን ለትውልድ መታመመ እንጂ።
ሶስተኛ    የመዝገበቃል አየለ “ግፍ አይሆንም?”፤ ፈጣሪ ተወርዋሪ ኮከብን አፈፍ አድርጐ ከጅራቱ የብርሃን ዝሃ መዞ የውብ ሴት ሽፋል ከኳለበት በኋላ ከመንደራችን ብታጐጠጉጥ እንዴት በዝሙት እንከሰስ? ለሴት ሰውር ስፌታዊ ውበት አለመቅበዝበዝ እንዴት ይቻላል በማለት ገጣሚው ዘይቤና ምስል እያፈራረቀ ፈጣሪን ይሞግታል።

Published in ጥበብ
Wednesday, 11 March 2015 11:09

ፀሐይ

(የአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት የአጭር ልብወለድ ውድድር አሸናፊ)

   በጠዋት መሥሪያ ቤት ስገባ ሰው ሁሉ የሆነ ነገር ሊነግረኝ ፈልጓል፤ የሆነ ነገር፡፡ ምን? ማወቅ አልቻልኩም፡፡ አለቃዬ ምን አዲስ ህግ አወጣ? ሰሞኑን ምን ተሳሳትኩ? ምን?  ለሳምንት ከከተማ ውጪ ነበርኩ፤ ግን በወጉ አስፈቅጃለሁ፤ ምን ሊሉኝ ይሆን? እየፈራሁ እነሱም እየፈሩኝ እንዲሁ የተለመደ የቃል ሰላምታ እየሰጠሁ ወደ ቢሮዬ ሽሽት …..
የአስተዳደር ቢሮውን አልፌ ፋይናንሶችን በርቀት ሰላም ብዬ፣ የቢሮዬን ቁልፍ ስጫን ሁሉ አንድ ነገር እየጠበቅሁ ነው፡፡ የሆነ ነገር ሹክ የሚሉኝ መሰለኝ፡፡ ገና ቁጭ እንዳልኩ ማርታ መጣች፡፡
 “አንቺ ዛሬ ምን ሆነሻል?” አለች፡፡ ምን ሆኛለሁ? እነሱ ገና ስመጣ ለምን ተያዩ?
“እ---ምንም-- ያው ታውቂ የለ-- ሰው ሰብሰብ ሲል አልወድም እኮ …” አልኩ፡፡
“እነሱማ ምንም ቢሆን ይመለከትሻል ብለው….”አለች፤ ያለ ሥራዋ ጠረጴዛዬ ላይ የተቀመጡትን የጽሕፈት መሣሪያዎች እያስተካከለች፡፡ ምንድን ነው እሚመለከተኝ?
“ማለት…”
“የዮኒን ነገር አልሰማሽም አይደል?” እጇ ከጠረጴዛው ላይ መንከላወሱን ሳያቆም አፍጥጣ እያየችኝ፡፡
“ምን ሆነ ዮኒ?”
 ዮናስ ባልደረባችን ነው፤ ራሱን ይኮፍሳል የሚል ስም ተሰጥቶት ብዙዎች ፊት እንደሚነሱት አውቃለሁ፡፡ አለቃችንም በተደጋጋሚ፤ “ለራስህ የሰጠኸውን ግምት አስተካክል፤ራስህን እንደ ፈላስፋ ታያለህ” ብሎታል፡፡ አባረረው እንዴ?
“ማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ ስትገቢ ምንም አላነበብሽም?” ጠየቀችኝ፡፡
 “አላነበብኩም” አልኳት፤መባረሩን እርግጠኛ ሆኜ፡፡
“ዛሬ በምሳ ሰዓት ቤቱ እንሔዳለን፤እናቱ እኮ አረፉ” አለችና ፊቷን ቅጭም አደረገች፡፡ ስለ ሞት ሲነገር ፊት እንዲህ ቁጥር ማለት እንዳለበት አጥንታለች፡፡
“ሞቱ?” ሳላስበው ጮኽኩ፡፡ በአካል አላውቃቸውም። እረፍት ከመውጣቴ ከአንድ ሳምንት በፊት ምሳ ሰዓት ላይ እንደተለመደው “እናቴ ቡና አፍልታ ምሳ አቅርባ እየጠበቀችኝ ነው” ብሎ ሔዷል፤ ከሳምንት በፊት ለእናቱ አንድ አዲስ የወጣ የልቦለድ መፅሐፍ አንብቦላቸው እንዳለቀሱ ነግሮኛል፤ ከአንድ ሳምንት በፊት የከሰዓት ሥራ መግቢያ የሰዓት ፊርማ ተነስቶበት፣እናቱ የድሮ የልጅነት ትዝታቸውን ሲያወሩለት እንዳረፈደ ነግሮኛል፤ ከሳምንት በፊት…..
ገና ብዙ ብዙ ጥያቄ ለማርታ ላቀርብላት ስል፣ ሔዋን በሩን በርግዳ ያፈነችው ሳቅ ፊቷን ወጥሮት ገባች፡፡
 “ዮናስ እኮ ዛሬ ሥራ ገባ” ብላ ሳቋን ለቀቀችው፡፡ የፊቷ ግት ረገበ፡፡ ማርታ በሳቁ አገዘቻት፡፡ ገና የመጀመሪያውን ሐዘን ከጉሮሮዬ ሳላወርደው፤ገና እየጮኽኩት እያለ  ሳቅ ይዘው መጡ፡፡
“ደህና አደራችሁ” በተከፈተው በር ዮናስ ገባ፡፡
የእነሱን ሳቅ የሰማ መስሎኝ ደንግጬ፤“ዮኒ አረፈድክሳ?” አልኩ፡፡ ምን ማለት ነው አረፈድክ ማለት? አላውቅም፡፡
“እ…ፂሜን እየተላጨሁ” አለ
ማርታና ሔዋን በሳቅ የተወጠረ ግታቸውን ይዘው፣ጥግ ፈልገው ከሌሎች ጋር ሳቅ ሊያልቡ ተሰወሩ፡፡ ሀዘን በጢም ውስጥ ብቻ ያደፍጥ ይመስል መላጨቱ እንደሚያስቃቸው ሳስብ በገንኩ፡፡ የእሱ የሀዘን ድምፅ ከሰላምታው ይጀምራል፡፡ “ደህና አደራችሁ” ሲል ድምፁ ውስጥ ሀዘኑ ታውቆኛል፡፡ ሁሉ ነገር እንደነበረ የማስመሰል ጥረት …. እሱ ግን ማስመሰል አያውቀውም ነበር፡፡
ቀና ብዬ ላየው አልደፈርኩም፡፡ ዝም ብዬ ሥራዬን ጀመርኩ፡፡ ዝም ብሎ ኮምፒውተሩን ከፈተ፡፡ ሁለታችንም የሒሳብ ባለሙያዎች ነን፡፡
ከሰዓታት በኋላ ሒሳብ ልክ አልመጣልኝ ሲል “……….” ብዬ ጠየቅሁት፡፡
“…….” ብሎ መለሰልኝ፡፡ ግን ልክ አልነበረም፡፡ እሱ ሒሳብ ተሳስቶ አያውቅም፡፡
ዮናስ እናቱ በሞቱ በሠልስቱ ሥራ ገባ፡፡ በየኮሪደሩ ተወራ፤
“ኸረ ምን አይነት አንጀት የሌለው ሰው ነው?”
“ሥልጣኔ ተብሎ ነው እንጂ….”
“የሆነ ልዩ ልሁን ባይ ነው-- ሲያስጠላ….”
“እና እንደ ደንቡ እናዋጣና ….” ስትል ገና አንዷ፤
“ኸረ ወደዛ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ….አሉ” ተቀባብለው፤ለሀዘኑ ክብር እንደሌለውና እሱን ማስተዛዘንም ክብር እንደሚነካ ተወያዩ፡፡
ምንም ሳልለው ቀናት ተቆጠሩ፡፡ በጠዋት ቢሮ ይገባል፡፡ ከእኔ ጋር ሰው ቢኖርም ባይኖርም “ደህና አደራችሁ?” ይላል፤መልስ አይጠብቅም፡፡ መልስ አይፈልግም፡፡
የሰላምታ ልማድ የለውም፡፡ ይኼ የሰሞኑ ትህትና ከየት መጣ?
በዝምታ እየሰራን ግር ሲለኝ እጠይቀዋለሁ፤ ይመልሳል ግን ትክክል አይሆንም፡፡ ስለ እናቱ አንዳች አልጠየቅሁም፡፡ እነ ማርታ፣ ቤት መምጣት እንፈልጋለን ብለውት፣አያስፈልግም እንዳለ ሰምቻለሁ፡፡
ከሳምንታት በኋላ ድንገተኛ ዝናብ አባሮኝ፣ዋቢ ሸበሌ ሆቴል በር ላይ ከዝናብ ተጠለልኩ፡፡ ዝናቡ ድንገተኛ አይመስልም፤ ቀና ብዬ ሰማዩን አየሁ፡፡ ሰማይ ላይ የግራር ሥር የመሰለ ነገር ብልጭ ብሎ ይጠፋል፡፡ ጃንጥላ የያዙ ሴቶች ሳይቀሩ እየተሯሯጡ ጥግ ይይዛሉ፡፡ በቅፅበት አስፋልቱ ጭር ብሎ ጥግ ጥጉን የቆመው ሰው ቆፈን ያሳደደው ቆጥ ላይ የወጣ ዶሮ መሰለ፡፡ መኪኖች ሳይቀሩ ደመናው ያዘለውን ዝናብ ሽሽት ጥግ እየያዙ ቆሙ፡፡ በኃይል ዘነበ፡፡ ጎርፉ የመኪኖቹን ጎማ ለመሸፈን ብዙ ደቂቃ አልፈጀበትም፡፡ ዘመኑ 2007 መሆኑን ህንፃዎቹና መኪኖቹ ባይኖሩ ማወቅ የሚቻል አይመስልም፡፡ ያ የኖህ ዘመን….
በዚህ መሀል አንድ ሰው ከሩቅ እጁን ኪሱ ከትቶ፣ አስፋልቱን እየተንቀባረረበት ጎርፉን እየለጋ ይመጣል፡፡
“አያችሁ ያንን እብድ--- ለእሱ ፀሐይ ወጥቷል” አለ አንዱ፤ ወንድ መሆኑን በድምፁ ብቻ አወቅሁ እንጂ በብዙ ዝናብ ፈሪ ሰው ተከልሎ አልታየኝም፡፡ ጭር ባለው አስፋልት ዝናብና አንድ ሰው ብቻ ነበሩ፡፡ ሰውየው እየቀረበ ሲመጣ አለባበሱ ሙሉ ነው፡፡ ፀጉሩ አናቱ ላይ ሰጥሟል፡፡ ፊት ለፊቱ መንገዱን እያየ እጁን ከኪሱ ሳያወጣ ይጓዛል…. እየተንቀባረረ…. ዝናቡን በካልቾ እየለጋ…… እያንቦጫረቀ…..
አልፎኝ ከሄደ በኋላ “ዮኒ” ብዬ ጮኽኩ፡፡ አልሰማኝም፡፡
“ዮኒ” ሮጥኩና ወደ ውሃው ገባሁ፡፡
ከኋላዬ ብዙ ሳቅ ነበረ፡፡
“ዮኒ…..ዮኒ…..” እያለከለኩ አስፋልቱን የሸፈነው ጎርፍ ውስጥ በቁሜ እየዋኘሁ፣ ነጭ ረጅም ቀሚሴ ከኋላዬ እየተንሳፈፈ ደረስኩበትና እጁን ያዝኩት፡፡ “ዮኒ…” ፈገግ ያልኩ ይመስለኛል፡፡
“እ--” ለአፍታ ቆም አለና አይቶኝ ትርጉም የሌለው ሳቁን ሳቀ፡፡ ድሮም ድንገት ይስቃል፤ሳቁ ልምድ እንጂ ስንቅ አይመስለኝም ነበር፡፡ መንገዱን ቀጠለ፡፡ እጁን እንደያዝኩ ተከተልኩት፡፡ ኖህ ፈርቶ ረጅም አመት ደክሞ የሰራው መርከብ አላስፈለገንም፡፡ በጎርፉ በቁማችን እየዋኘን ወደ ፊት አልን፡፡
በዝምታ ጥቂት እንደተጓዝን፤ “ቁርስ ግን በልተሃል?” አልኩት፤የምለው ጠፍቶኝ እንጂ ቁርስ እንደማይወድ አውቃለሁ፡፡  
“እንደ ዛሬም በልቼ አላውቅ” ሲል የሚያሾፍ መሰለኝ፡
“ፀሐይ ከሞተች ጀምሮ ቁርስ ሳልበላ ወጥቼ አላውቅም ” ሲል ግር አለኝ፡፡
“እንዴ -- ድሮ ማዘር ስለማይሰጡህ ነበር ማትበላው?” አልኩ፤ለቅሶ ሳልደርሰው፣ ቁጭ ብዬ ሳላዋየው ደፍሬ ስለ እናቱ ሳወራ ለምን እንዳልከበደኝ አላውቅም፡፡  
“እሷ ቁርስ እንደማልወድ ታውቃለች”
“እና አሁን ወደድክ?”
“እሷ እያለች እኮ ‘ማልበላው ለምሳ ስመለስ፣ ቡና አቀራርባ ቁርስ አዘጋጅታ እንደምትጠብቀኝ ስለማውቅ ነው፡፡ አሁን ቁርሴን ባልበላ ድጋሚ ምግብ ለማግኜቴ ምን ዋስትና አለኝ?” አለኝና ያን የማልወደውን ሳቅ ሳቀ፡፡
“እ… ከባድ ነው” አልኩ፤ኪሱ የወሸቀውን ክንዱን እንደያዝኩ፣ጎርፍ እያጀበን ቀሚሴን እያንሳፈፍኩ እንሄዳለን፡፡
“ከባድ ብቻ ?” መልሶ ጠየቀኝ፡፡
“ፀሐይን ለዘላለም እንደማላገኛት እርግጠኛ መሆን ከባድ ብቻ?” አለ
“አንተ እኮ ቶሎ ሥራ መግባት የለብህም ነበር፤ፈቃድ ወስደህ ትንሽ ጊዜ ብታርፍ--” በዚያውም ከሰው ትችት ባድነው ብዬ የሰነዘርኩት ሃሳብ ነው፡፡
“ምን ላድርግ ቤት መዋል አልቻልኩም፤ ሰዎች የእናቱን ሀዘን ሳይጨርስ በሰልስቱ ቢሮ ገባ ይላሉ፤እኔ እኮ ግን እስካሁን ቢሮ የለሁም ” አንዴ ብቻ ከደረት ተነስታ ሳቅ መስላ የምትወጣ ጩኸቱን አሰማ፡፡
“እሳቸው ሲሞቱ አንተ የት ነበርክ?”
“ቢሮ… ቢሮ ነበርኩ” አለ ችኩል ብሎ
“ተደውሎልህ ነዋ?”
“ጎረቤቶቻችን ደውለው-- ና --- ፀሐይ አሟታል አሉኝ፤ ደንግጬ ወዲያው ወጣሁ…አንዳንዴ ልቤ ላይ ወጋኝ ብላ ጥቂት አረፍ ስትልበት ይለቃታል፡፡ ባሰባት ማለት ነው? እያልኩ ሰፈራችን ያለ ጤና ጣቢያ ስበር ደረስኩ፡፡ የሰፈሬ ልጆች እዚያው አካባቢው ዮኒ ሰላም ነው ብለው አክብረው ሰላም ሲሉኝ መደንገጥ ጀመርኩ፤ እንዲህ ተከባብረን አናውቅማ…ወደ ጤና ጣቢያው ስገባልሽ፣ እነ ወ/ሮ ትብለፅ ሁሉ ነጠላቸውን አዘቅዝቀው አደግድገው ….” የያዝኩት እጁ የተንቀጠቀጠ መሰለኝ፡፡
“ምንድን ነው ፀሐይ የታለች-- የታለች እናቴ-- እያልኩ በኃይል ጮኽኩ፤ ቁጭ በል ቁጭ በል እያሉ ብዙ እጆች ሊያንበረክኩኝ ይጥራሉ፡፡ እኔ ዝም ብዬ የታለች ፀሐይ-- የታለች-- ስል አንዷ ጎረቤታችን ሞታለች ዮናስ ቻል አድርገው አለች፡፡ እንዲህ ማለቷን ከሰማሁ በኋላም የታለች  ፀሐይ፤ የታለች እላለሁ ዝም ብዬ” አለና ያን እርጉም ሳቁን ሳቀ፡፡
ዝም አልኩት፡፡
“ከዛ ወጥቼ ሮጥኩ”
“ወዴት?”
“እንጃ ግን ከጤና ጣቢያው ግቢ ዝም ብዬ እየሮጥኩ ወጣሁ….እነዛ መንገድ ላይ በአክብሮት ሰላም ያሉኝ አብሮ አደግ ጓደኞቼ ከየት እንደመጡ እንጃ ያዙኝ” እጁ በኃይል ተንቀጠቀጠ፡፡ የእኔ እንባ ከዝናቡ ጋር ፊቴን ያጥበዋል። እሱ እያለቀሰ ያውራኝ እንዲሁ ያውራኝ መለየት አልቻልኩም፡፡
“እናቴን እንደ ወንድ ልጅ ጋቢ ተከናንቤ-- ፊቴን አጥቁሬ-- ሰው እየተከተልኩ አይደለም የሸኘኋት-- ሰውነቴ ሁሉ ውሃ እስኪመስለኝ ድረስ አልቅሻለሁ፡፡ እንባዬ ለአፍታ እንኳን ለዘላለም የሚቆም አልመሰለኝም ነበር-- እሁድ ሰውነቴ ድቅቅ ብሎ እንቅልፍ እንቅልፍ ሲለኝ ዋለ፤ ሰኞ በጠዋት ሰዎች መ‘ተው አሟት ነበር? ብለው መላልሰው ሲጠይቁኝ --- ምን ላድርግ? ብድግ ብዬ ቢሮ ሄድኩ” አለና ዝም አለ፡፡
‘አይዞህ ሞት በሁሉም አለ፤ ዋናው በህመም አለመሰቃየታቸው ነው፣ እኛ ሁላችንስ ወደዚያው አይደለን …’ ልለው አሰብኩና ተውኩት፤ ሁሉም ቃላት አጉል እኔን ያደክሙኛል እንጂ እሱን አያፅናኑትም፡፡ ዝም እንዳልኩ እሱ ቀጠለ፡፡
“እሷ እያለች የማታውቀው ነገር ሁሉ ላይ አሁን የሚያገባት ይመስለኛል፤ አሁን ይኼ ዝናብ እሷ ስለሌለች ሆን ብሎ የሚመታኝ ይመስለኛል፡፡ ሰማዩ ብልጭ ሲል ሆን ብሎ እሷ ስለሌለች ሊያስደነግጠኝ የፈለገ ይመስለኛል፡፡ እሷ ከሞተች ጀምሮ እንኳን የቤቱ የሆቴል ቤቱ የምግብ ጣዕም የተለወጠ ይመስለኛል… እሷ እኮ ግን ያን ሆቴል ጨርሶ በእግሯ ረግጣው አታውቅም” ብሎ ያችን ሙት ሳቁን ሳቀ፡፡
“ሞት እንዲህ ከባድ ይሆናል ብዬ አስቤ አላውቅም፡ ለእናቴ እንዲህ ሳላደርግላት፣ እንዲህ ሳልሆንላት የምለው ነገር ኖሮ አይደለም በጣም ያዘንኩ፤ ግን በቃ ናፍቆቷን አልቻልኩትም፤ በጣም በጣም ትናፍቀኛለች… እናቴ በተለይ ምሳ ሰዓት ላይ ቡና አፍልታ ስትጠብቀኝ ጎረቤት እንኳን አትጠራም ነበረ፡፡ ለእነሱ ሆን ብላ ጠዋት ጠዋት ቡና ታፈላለች፡፡ ለምን እንደሆን ታውቂያለሽ? እኔ እና እሷ ብቻ ስንሆን ደስ ይላታል፡፡ ልጅነቷን ታወራኛለች፣ ልጅነቴን ታወራኛለች፣ አንዳንዴ ደግሞ መፅሐፍ አነብላታለሁ … ቀብር ወይ ሌላ አስገዳጅ ነገር ካልገጠማት እናቴ በህይወቷ የማስታስተጓጉለው ቀጠሮ ምሳ ሰዓት ከእኔ ጋር ማሳለፍን ነው፡፡ ፀሐዬ እኮ ምንም ደብቃኝ አታውቅም ነበረ፡፡
አየሽ ያን ቀን እንደምትሞት አለማወቋ እንዴት እንደሚያስጠላ? ብታውቅ እኮ ቁርሴን በግድ ታበላኝ ነበር፤ ሌሊቱን ሳንተኛ የጀመርኩላትን መፅሐፍ እጨርስላት ነበር፣ቡናውን በጠዋት ተነስተን እንጠጣ ነበር…” አለና አሁንም ሳቀ፡፡
ሄደን ሄደን ጦር ኃይሎች ደርሰናል፡፡ ዝናቡ አባርቶ ልስልስ ያለች የማትጠገብ ፀሐይ ወጣች፡፡ እጁን ለቅቄ ንክር ልብሴን  መጭመቅ ያዝኩ፡፡
“አየሻት ፀሐዩዋን--ጭፍግግ ያለውን ሰማይ እንዴት በፈገግታ እንዳጥለቀለቀችው አየሽ…” ቀና ብዬ ሰማዩን እንዳይ ወተወተኝ፡፡
ረጅም መንገድ ሲያለቅሱ የነበሩ ዓይኖቼ ፀሐዩን መቋቋም ስላልቻሉ እንዳንጋጠጥኩ ጨፈንኳቸው፡፡
“አየሽ የኔ ፀሐይም-- የኔን በሥራ -- በኑሮ የደከመ ልብ ምሳ ሰዓት ላይ እንዲህ ነበር ወገግ የምታደርገው” ሲል አይኔን እንደጨፈንኩ የእሱን ፀሐይ አየሁ፡፡

Published in ጥበብ

የሥነጽሁፍ ውድድር አሸናፊዎች ይሸለማሉ
የአሰፋ ጎሳዬ የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ይመረቃል

   ሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ የተመሠረተበት 15ኛ ዓመት በዓል የፊታችን ሰኞ ከ11 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡ በበዓሉ ላይ አንጋፋና ወጣት ገጣሚያን ስራዎቻቸውን  የሚያቀርቡ ሲሆን ለአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት በዓል በተዘጋጀው የሥነ ጽሁፍ ውድድር በአጭር ልብወለድና በግጥም ከ1-3 የወጡ አሸናፊዎች ይሸለማሉ ተብሏል፡፡
የአዲስ አድማስ መሥራችና ባለቤት የነበረው የአቶ አሰፋ ጎሳዬን ህልምና ራዕይ የሚያስቃኝ “የአዲስ አድማስ ሰው” የተሰኘ መጽሐፍም በዕለቱ ይመረቃል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የመጀመሪያ ዕትም ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ለንባብ የበቃ ሲሆን በዕለቱ የወጣው ርእሰ አንቀጽ፤ “የአዲስ አድማስ ዓላማ ኢንፎቴይመንት ነው፤ኢንፎርሜሽን ሰጪ-ቀልድና መዝናኛ” ሲል አስፍሯል- የዛሬ 15 ዓመት፡፡

በደራሲ፣ገጣሚና ተዋናይ ዋሲሁን በላይ (አዋበ) የተፃፈው “የሴት ዛፍ ቅርንጫፍ” የተሰኘ የታሪኮች መድበል በገበያ ላይ ዋለ፡፡ መጽሐፉ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ታሪኮች በግጥም ታጅበው ቀርበውበታል፡፡ በ208 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ፤በ45 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን ገጣሚው ከዚህ ቀደም “አልገባም ጐጆዬ” ፣ “ጠይም ደም” እና “የአንድ አይን እምባ” የተሰኙ የግጥም መጽሐፍትን ለአንባቢያን ማድረሱ ይታወሳል፡፡

በመጋቤ ብሉይ ዳንኤል አጥናፉ የተዘጋጀው “የግዕዝ ውቅያኖስ ሲጨለፍ” የተሰኘ መጽሐፍ ከትላንት በስቲያ በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዳራሽ ተመርቋል፡፡ በርካታ የግዕዝ ቃላትን ከነፍቺያቸው የያዘው መጽሃፉ፤የግዕዝ ቋንቋን መማር ለሚፈልጉ በእጅጉ እንደሚያግዝ ተጠቁሟል። መጽሐፉ ከመመረቁ ከአንድ ሳምንት በፊት ለገበያ መቅረቡ ታውቋል፡፡
 “የውጭ ቋንቋን እንደ ንፁህ አየር እየማጉ የራስን ቋንቋ እንደተቃጠለ አየር ወደ ውጭ ማስወጣት፣ማንነትን በፈቃደኝነት ለምርኮ መስጠት ነው”፣እንግሊዝኛን እየተማሩ ግዕዝን አለመማር፣ እንግሊዝን እያቀፉ ኢትዮጵያን መግፋት ነው” ያሉት መጋቤ ብሉይ ዳንኤል፤ ሁሉም ለግዕዝ ቋንቋ ትኩረት ሰጥቶ እንዲማር መክረዋል፡፡ በመቶ ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ በ30 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መጋቢ ብሉይ ዳንኤል አጥናፉ፤በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉይ ኪዳንና የልሳነ ግዕዝ መምህር ሲሆኑ በማታው የትምህርት መርሃ ግብር የትምህርት ክፍል ሃላፊ እንደሆኑም ታውቋል፡፡

በአንጋፋዋ የኪነ - ጥበብ ባለሙያ አለምጸሀይ በቀለ ተደርሶና ተዘጋጅቶ በጄአይዲ የኪነጥበብ ፕሮሞሽንና ቴአትር ኢንተርፕራይዝ  የሚቀርበው “ወንድ አይገባም” የተሰኘ ሳታየር ኮሜዲ ቴአትር የፊታችን ሰኞ በሐገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከ11፡00 ሰዓት ጀምሮ ይመረቃል፡፡
እያዝናና ያስተምራል በተባለው በዚህ ቴአትር ላይ አንጋፋና ወጣት ተዋንያን የሚሳተፉ ሲሆን ጀምበር አሰፋ፣ ቅድስት ገ/ስላሴ፣ መሰረት መኮንን፣ መክሊት ገብረየስ፣ ማርታ ጌታቸው፣ ባንቺአምላክ ስለሺና ሌሎችም ይተውኑበታል፡፡ ቴአትሩ ከነገ ወዲያ በሐገር ፍቅር ከተመረቀ በኋላ ዘወትር ሰኞ በዚሁ ቴአትር ቤት ለተመልካች መቅረብ ይጀምራል፡፡  

Monday, 09 March 2015 12:13

በአዲስ አድማስ ዋዜማ

ሁሉም ነገር የሆነበት ጊዜ ወደ ሁዋላ እየራቀ ሲሔድ ለዛሬ ሕልም መምሰሉ አይቀርም።  ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ግማሽ ጐኑን ተረት ይበላዋል። ለእንደኛ አይነቱ ፅፎ ማስቀመጥ ብዙ  ለማይሆንለትማ ጭራሽ በመረሳት ጎርፍ  የሚጠረግበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም።
እንዲህ ሥራውን አክብሮ መሰረቱን አሳምሮ ቀና እንዳለ፣ አስራ አምስት አመታትን አስቆጥሮ ዛሬ የደረሰው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ የዛሬ አስራ አምስት አመት  ረዥም ጉዞ የማይታክተው ቁምነገረኛ ጋዜጣ ጀምረን  እስቲ ሳናቋርጥ ማሳተም ያቅተንም እንደሆን፣ ሞክረን አቅማችንን ካላየን ምን ዋጋ አለው ? በሚል ወኔ  ባለቤቱ  አሴ - አሰፋ ጎሳዬ መውጣት መውረድ ከጀመረ ሰንበትበት ብሎ ነበር። ታዲያ ምንም እንኳ አብዝቶ የሚገናኘውም የሚመክረው ከቆየ የስራም የሐሳብም ባልደረባው ከጌታ መኮንን ጋር ቢሆንም በተለይ ከስራ በሁዋላ አመሻሽ ላይ በዋዛውም በቁም ነገሩም ከሚቀላቀሉት መካከል   እኔም አንዱ ነበርኩ።
 ከዚያ ቀደም ብሎ  አምስት ስድስት ዓመት በፊት ገደማ  “አዲስ አርት ፌስቲቫል” የተሰኘውን በሐገሪቱ የመጀመሪያውን  ሳምንት ሙሉ የተካሔደ ዙሪያ መለስ የስነ-ጥበብ ፌስቲቫል ለማዘጋጀት ጌታ መኮንን አሰባስቦ ካስተዋወቀን ምርጥ ሰዎች አንዱ ነበር- አሴ ። እርሱ ሰዓሊ ወይ ገጣሚ ባልሆነበት ሌሎች ታውቀው እነርሱው  በሚጠቀሙበት የሳምንት ሙሉ ትልቅ ክብረ-በዓል በአዲስ አበባ ይካሔድ ዘንድ የከሰረው የገንዘብ መጠን፣ ያባከነው የጊዜ ብዛት፣ የወጣ የወረደበት ቦታ፣ የተለማመጠው የለመነው የሰው ብዛት፣ በዚያም ያገኘውን የመንፈስ ደስታ አሁንም ድረስ ሳስበው   ካለማቸውና  ካከናወናቸው ተግባራቱ ሁሉ
 የታዘብኩት በርግጥ ሰውና ሐገሩ  መለወጥ ካማራቸው የምር መለወጫ መንገዱ ይኸው መሆኑን ነው
ርዕይ ፣ ዛሬ እንደ ብይ መጫወቻ ሳይሆን ርዕይ ከተባለ በበኩሌ የአሴ አይነት ርዕይ ያለተጨማሪ ማብራሪያ ምን እያሉ ምን ማድረግ እንደሆነ ያኔም አሁንም በቀላሉ ይገባኛል። አዲስ አርት ፌስቲቫል እስከ ዛሬ ያልደበበዘዘውን አሻራ ጥሎ እንዲያልፍ ከጌታ መኮንን ጋር ሁሉን ካደረጉ  በሁዋላ፣ አሴ በአንድ ወይ በሌላ መልክ ቋሚ የሆነ የእውቀት ወይም የጠቅላላ መረጃ መድረክ መፍጠር ወይም ከዚያም በላይ “ትልቅ የሆነ ነገር ላገራችን በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን ? ” ዓይነት ነገር የሁልጊዜ ጥያቄና ጨዋታው ነበር። ለራሱ
ስራ ፈጥሮ ብዙ ብዙ መንገዶችን በብዙ ሌሎች መስመሮች በኩል ደጋግሞ  እንደሞከረ
 አስታውሳለሁ። ሁሉንም የገንዘብ ትርፍ አጥቶባቸው ሳይሆን እርሱ “ሐገር” ፣ “ ወገን” ከሚለው ኅብረተሰብ ጋር አብሮ ከማደግ ፣ አውቆ ከማደግ ጋር በልቡ ያለውን ሕልም አልፈታ ስላለው ብቻ ነው ጥሎ ሌላ ለመጀመር የሚደክመው ። ይህ አይነቱ የአስተሳሰብ ሐብት ዛሬ አሰፋ ካለፈ በሁዋላ በኖርናቸው ጥቂት አመታት ውስጥ በብርሃን ፍጥነት  አሽቆልቁሎ፣ የከፋ ኪሳራ ውስጥ እንደምንገኝ አጥብቄ አምናለሁ። ከዚያ አንፃር ከተመዘንን፣ ስንቶቻችንና ማንኛችን ሞተን፣ ማንኛችን ደግሞ  የኗሪነት ቆጠራ እንደሚመለከተን አላውቅም።
ከብዙ ማውጣትና ማውረድ፣ ከብዙ ምክርና ማሰላሰል በሁዋላ  ያ የመረጃ መድረክ ጋዜጣ ቢሆን እንደሚያስኬድ ከዚያም ቀስ በቀስ የኢትዮጵያን ስነ-ጥበብ ሊያግዝ የሚችል አቅም የሚኖረው ተቋም ራሱ ይፈጥራል ተብሎ ጋዜጣው ይቅደም የሚል ውሳኔ ላይ ተደረሰ። ሁልጊዜም አሰፋ በስነ-ጥበብ ውበትና ጉልበት ላይ እምነት ነበረው። በዙሪያው በነበርነው የሙያው ሰዎች ተፅዕኖ አይመስለኝም። ዋናው ምክንያት ከገዛ ስልጣኔው የመነጨ እንደሆነ እኔ ጥርጣሬ የለኝም ። ስልጣኔው ስል  መማሩ ብቻ ማለቴ  አይደለም ። በመማርብቻ መሰልጠን እንደማይገኝ ከብዙ ምሁራኖቻችን ስለምናስተውል። ይልቁንም  አሰፋ ሲበዛ አንባቢ ፣ ምን  እንደሚያነብም የሚያውቅ ፣ በጥልቅና በፍጥነት ማንበብ የሚችልበት፣ የሚያነበው ለባላጋራ ማጥቂያ ወይም ያደባባይ  መኮፈሻ  ሳይሆን በቃ ለዕለት ተለት የአይምሮ ምግቡ  እየሰፈረ የሚመገበው ነው። ከዚያ የሚገኘውን ጉልበት እንዴት  ለሕይወት ጥያቄዎች መልስ መፈለጊያነት  እንደሚተረጉመውም አሳምሮ ያውቅበታል። እንኳን ከመፅሀፍ ከጉዋደኛ የሰማውን በራሱ እውቀትና ባካባቢው አቅምና ቋንቋ  አዋዝቶ  ያወርደዋል እንጂ አንዱንም  በደረቁ  ቃል በቃል ደግሞት አያውቅም። ለዚህ አይነቱ ሰብዕና   ስነ- ጥበብን ማወቅም ሆነ ማድነቅ፣ ማክበርም ሆነ መደገፍ እንግዳም ትርፍ ነገርም አይሆንም ።
አንድ ቀን ምሽት ጋዜጣው ሊታተም በጣም ጥቂት ቀናት ሲቀሩት፣ እነ አሰፋ በርከት ብለው ከሚያወኩበት ቦታ ስልክ ካንዳቸው ዘንድ ይደወልልኛል። ጌታ ይመስለኛል ደዋዩ። “አሁን ርዕሱ ላይ ደርሰናል። አሁን ሁላችንም  የወደድነውንና ጥሩ የመሰለንን ርዕስ እየሰነዘርን  ነው። ለምሳሌ  አዲስ ….. “ ብሎ ሳይጨርስ ካፉ ቀልቤ …” በቃ እንግዲህ  ጀመራችሁ ገብረ-ማርያም ሲባል ወልደማርያም ማለት ደስ አይልም …አዲስ ዘመን እዚያ ጋ ስለሚታተም እዚህ  ጋ የግድ አዲስ -ዓለም ፣ አዲስ-ማተብ እያልን መቀጠል አያምርብንም--”
እያልኩ  ትንሽ ተሞጣሞጥኩ። በስብሰባም ይሁን በሻይ ጨዋታ ላይ፣ ነገራችን  ሁሌም
 ከድርቀት የነፃ ነበር። “በመሰረቱ-- በዋናነት---በአዋጭነት ….” ብሎ ንግግርን ፊት ሰጥተነው አናውቅም።
በዚያ ምሽት ካልዘነጋሁ እነ ነቢይ፣ እነመስፍን እና ሌሎችም አብረው የነበሩት ሁሉ ብዙ ቀልዶችና ሐሳቦች ሰነዘሩ ።ግፋ ቢል ሁለት ቀናት ፈጀ መሰለኝ ፣ ወዲያው የመጀመሪያዋ አዲስ አድማስ ታትማ ወጥታ፣ ሁላችን በጣም ተደሰትን ። ያኔ ያሽሟጠጥኩባት “አዲስ”  እነሆ  ከዚያም በሁዋላ  ስንትና ስንት  አዲሶችን ፈለፈለች ። አዲስ ነገር ። አዲስ ጉዳይ …..እና ሌሎችንም።

Published in ጥበብ