ኢህአዴግ፣ መድረክና ኢዴፓ ያካሄዱት የመጀመሪያው የምርጫ ክርክር፣ ብዙም ትኩረት ሳያገኝ ማለፉ ያሳዝናል። በጥሞናና በንቃት ልንከታተለው ይገባ ነበር። በእርግጥ አዝናኝ አይደለም፤ አሰልቺ ነው። ቁምነገረኛ ሃሳቦች፣ ጠርተውና ጎልተው የወጡበትም አልነበረም። የፓርቲዎቹ ክርክር በትኩረት ብንከታተል ኖሮ፣ ትልልቅ ሃሳቦችን፣ መሳጭ ማብራሪያዎችን፣ አነቃቂ ራዕዮችን እናገኝበት ነበር ማለቴም አይደለም። የፓርቲዎቹን የሃሳብ ልዩነት ለማየትና የትኛው ፓርቲ ከየትኛው እንደሚሻል ለማመዛዘን እድል ይሰጣል ማለቴም አይደለም። በተቃራኒው፣ የአገራችን ፓርቲዎች ያን ያህልም የተራራቀ አስተሳሰብም ሆነ የተራራቀ ሃሳብ እንደሌላቸው በቀላሉ የምናይበት ጥሩ አጋጣሚ ይሆንልን ነበር። በተመሳሳይ የአስተሳሰብ ቅኝት የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች የቱን ያህል ተመሳሳይ እንደሆኑ ማየት በቻልን ነበር። እንዲያውም፤ ተመሳሳይ ሃሳባቸውን ለመግለፅ፣ ተመሳሳይ ቃላትና ሃረጋትን ነው የሚጠቀሙት።
በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻና ቁጥጥር በማሳነስ ነፃ ገበያን ማስፋፋት ያስፈልጋል የሚለው የ“ሊበራሊዝም ወይም የካፒታሊዝም አስተሳሰብ”፤ “የኒዮሊበራሊዝም አስተሳሰብ” ተብሎም እንደሚታወቅ የጠቆሙት የክርክር መድረኩ ተሳታፊ፤ “የገበያ አክራሪነት” ሲሉ ፈርጀውታል። “ደሃውን የበለጠ ድሃ እያደረገ፣ ሃብት በተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲያዝ እያደረገ” ነው በማለትም አውግዘውታል። ይሄ አዲስ ውንጀላ አይደለም። ራሳቸውን ከሶሻሊዝም አባዜ ለማላቀቅ ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ዘወትር የሚያሰራጩት ውግዘት ነው። “ነፃ ገበያ የሃብት ልዩነትን ስለሚያሰፋ፣ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ሃብት ያከፋፍል፤ ከዜጎች የስራ ገቢ ገሚሱን እየወሰደ ለድሆች ድጎማ ይስጥ” ለሚለው ዲስኩር ፈፅሞ እንግዳ አይደለንም። እኚሁ የክርክር ተሳታፊ ግን፣ ልክ እንደ አዲስ ግኝት፤ ዛሬ ዛሬ በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ሚና በአውንታዊነት መታየት” መጀመሩንም አብስረዋል።
እንዲያው፣ እውነታውን ለመደበቅ ነገሩን በከንቱ እያድበሰበሱ ያወሳስቡታል እንጂ፤ የካፒታሊዝም ወይም የነፃ ገበያ ስርዓት መሰረታዊ ሃሳብ ግልፅ ነው - “እያንዳንዱ ሰው በሰላምና በፍትህ እንዲኖር፤ በጥረቱ ፍሬ ላይ የባለቤትነት መብቱ ይከበር። ምርቱን ይጠቀሙበታል፤ ወይም ይገበያይበታል፤ ወይም በልግስና ለሌላ ሰው ይሰጣል፤ ውሳኔው የራሱ ነው”። በቃ ይሄው ነው፣ መሰረታዊው የነፃ ገበያ ሃሳብ። ቁልጭ ያለ ፍትሐዊ ሃሳብ ቢሆንም፤ ግን ብዙዎቻችን ልንቀበለው አንፈልግም። በተቃራኒው፤ የስራ ሰዎች በራሳቸው ጥረት ሕይወታቸውን ለማሻሻል የሚያመርቱትን ነገር፣ ልክ እንደራሳችን ንብረት ገሚሱን እየወሰድን ለሌሎች የማከፋፈል ‘ስልጣን’ እንዲኖረን እንፈልጋለን። በሌሎች ሰዎች ምርትና ንብረት ላይ አዛዥ ናዛዥ መሆን ያምረናል። እና ይህንን የቅሚያ ስርዓት፤ “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል”፣ “ማህበራዊ ፍትህ” እያልን እንጠራዋለን።
በእርግጥ ገና ድሃ የሆነች አገር ውስጥ፣ ከሃብት ክፍፍል በፊት ሃብትን ማመንጨት እንደሚቀድም ጠቅሰዋል - የክርክሩ ተሳታፊ። ሶሻሊስቶች “ነፃ ገበያን፣ ካፒታሊዝምን፣ ሊበራሊዝምን” ለማንቋሸሽ የሚያዘወትሯቸው አገላለፆችን በመጠቀም፣ ‘ሊበራሊዝም ወይም ኒዮሊበራሊዝም የገበያ አክራሪነት ነው’ በማለት የተናገሩት እኚሁ ተሳታፊ፤ ተጨማሪ ጥላሸት ሳይቀቡ አላለፉም። ሊበራሊዝም፣ “ግለሰብን ልክ እንደ እንጉዳይ ብቻውን... የበቀለና በራሱ ምሉዕ አድርጎ የሚያስብ ነው። አንድ ግለሰብ ግን ምሉዕ ሰው የሚሆነው ... ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ ነው” በማለት አጣጥለውታል።
ከየትኛው ተሳታፊ ነበር ይህ ትችትና አቋም የተሰነዘረው? ኦ... ይቅርታ። ተከራካሪ የፓርቲ ተወካዮች አይደሉም ይህንን የተናገሩት። የክርክር መድረኩን በገለልተኝነት ለማስተናበር የተሰየሙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁር ናቸው ይህንን አቋማቸውንና ትችታቸውን ያቀረቡት። በአሽሙር ቢጤ፣ ምሁሩን እየተቸሁ እንዳይመስላችሁ። ያልተለመደና እንግዳ የሆነ ስህተት አልፈፀሙም። ለካፒታሊዝም ወይም ለነፃ ገበያ ያለን ጥላቻኮ፣ የረዥም ዘመናት ቅርሳችን ነው። በትጋት ሃብት የሚያፈራ ሰው አይወደድም። የዚህ ጥንታዊ ባህል ዋና ጠበቃ ሆነው በፍቅር እስከ መቃብር መፅሐፍ ላይ የተገለፁት ፊታውራሪ መሸሻ፣ ለሃብታሞች የነበራቸውን ጥላቻ የምታውቁት ይመስለኛል። በጥረት ሃብት ያፈሩ ሰዎች ናቸው፣ የጥላቻው ኢላማዎች።
በዚህ ጥንታዊ ባህል ላይ፣ የሶሻሊዝም አስተሳሰብ ተጨምሮበት፣ አብዛኛው ዜጋ፣ አብዛኛው ፖለቲከኛና ምሁር የነፃ ገበያ ጠላት ቢሆን አይገርምም። በሌላ አነጋገር፣ ክርክሩን ያስተናበሩ ምሁር፣ ገለልተኛ አይደሉም ብሎ መተቸት አስቸጋሪ ነው። እንዴት በሉ።     
ስለመንግስት ጣልቃ ገብነትና ሚና፤ ስለሃብት ልዩነትና ክፍፍል፣ ከተከራካሪ ፓርቲ ተወካዮች የተሰነዘሩ ተመሳሳይ አስተያየቶችንና አቋሞችን ተመልከቱ። በእርግጥ፣ ኢህአዴግ፣ መድረክ እና ኢዴፓ ሦስት የተለያዩ አስተሳሰቦችን የሚከተሉ ፓርቲዎች እንደሆኑ ተደርጎ ነው የቀረበው - አንዱ የልማታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ፣ ሌላኛው የሶሻል ዲሞክራሲ፣ ሦስተኛው ደግሞ የሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ። ግን፣ ብዙም አይለያዩም። ሦስቱ ፓርቲዎች የየራሳቸውን አስተሳሰብ በማሞገስና ትክክለኛነቱን በመግለፅ የተናገሩትን ሃሳብ ልጥቀስላችሁ። ሁሉም፣ “የሐብት ክፍፍል” እና “የመንግስት ጣልቃ ገብነት” እንደሚያስፈልግ ይሰብካሉ።
ተከራካሪ ቁ.1
“የአገሪቱን ሃብት በአጠቃላይ ህብረተሰቡ እኩል የሚከፋፈልበትና የሚያድግበትን የልማት አቅጣጫ የሚከተል ነው” በማለት የፓርቲያቸውን አስተሳሰብ ያወደሱት አንደኛው ተከራካሪ፣ በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል - “ከድህነታችን አኳያ በህግ በተገደበ አኳሃን የመንግስት ጣልቃ ገብነት [ማስፈለጉ] ምንም የሚያጠራጥር አይደለም” በማለት።
የየትኛው ፓርቲ ተወካይ ይሆኑ? ምናልባት፣ “እኩል የሃብት ክፍፍል” እና “በተመረጠ አኳሃን የመንግስት ጣልቃ ገብነት” የሚሉ አባባሎችን ስታዩ፣ በእርግጠኛነት የኢህአዴግ ንግግር ነው ትሉ ይሆናል። ግን አይደለም። የኢዴፓ ተወካይ ዶ/ር ጫኔ ከበደ የተናገሩት ነው።
ተከራካሪ ቁ.2
የሃብት ክፍፍል እንደሚያስፈልግ በምሳሌ ጭምር ያስረዱት ሌላኛው ተከራካሪ፣ “ሃብት ማካበት በቻለው መካከልና በቀረው ተራ ህዝብ መካከል ያለው ልዩነት ይህን ያህል ሊራራቅ አይገባም”  በማለት ሲያስረዱ፤ “ግብር ሰብስቦ የሚያስተዳድረው መንግስት ሚና ሊኖረው ይገባል” ብለዋል። በአንዳንድ አገራት የሰዎችን ኑሮ ለማመጣጠን ከዜጎች ገቢ ግማሽ ያህል በታክስ እየተቆረጠ መንግስት እንደሚወስድ እኚሁ ተከራካሪ ጠቅሰው፤ “ይህ ግን ኅብረተሰቡን የሚያሳስበው ሆኖ አልተገኘም። ምክንያቱም ጽዳት ሰርቶም ኖረ፣ የህክምና ባለሙያም ሆነ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ኑሯቸው ተመጣጣኝ ስለሆነ... በደስታ ነው የሚኖሩት” ብለዋል።
የህክምና ዶክተርና የፅዳት ሰራተኛ ተመሳሳይ ገቢ እንዲኖራቸው ማድረግ አስደሳች ሲሆን ይታያችሁ። የአገራችን ሃኪሞች፣ ወደ ውጭ የሚጎርፉት አስደሳች ኑሮ እየሰለቻቸው መሆን አለበት። እዚህ ካሉት ሃኪሞች ይልቅ በዋሺንግተንና በአቅራቢያዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሃኪሞች በቁጥር እንደሚበዙ አልሰማንም ማለት ነው?
የሆነ ሆኖ እኚህ ተከራካሪ በምሳሌነት የጠቀሷቸው አገራት አስገራሚ ናቸው፤ የእነዚያ አገራት ሰዎች ልዩ ፍጡራን ሳይሆኑ አይቀሩማ - ጥረው ግረው ካገኙት ገቢ 50% ታክስ ቢቆረጥባቸውም አያስጨንቃቸውም፤ ለምን? እኚህ ተከራካሪ ምላሽ አላቸው፤ “ለጋራ ሕልውናና ጥቅም የሚደረግ መስዋዕትነት... የሰው ፍጡር አንዱ ከሌላው እጅግ በሰፋ ሁኔታ መኖር የለበትም ብለው ነው የሚያምኑት” በማለት እኚሁ ተከራካሪ የሃብት እኩልነትንና የመንግስት ጣልቃ ገብነትን አወድሰዋል።
እኚህ ተከራካሪስ ከየትኛው ፓርቲ የመጡ ይሆን? “የጋራ ሕልውና፣ መስዋዕትነት፣ የሃብት ክፍፍል፣ በግብር ከፋይነት መደሰት፣ የመንግስት ሚና” ... እነዚህን ቃላትና ሐረጋት ስትመለከቱ፣ የየትኛው ፓርቲ አባባሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያቅታችሁም። የኢህአዴግ ነዋ። አይደለም እንዴ? ይቅርታ፣ ተሳስቻለሁ። የመድረክ አመራር አባል የሆኑት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ከተናሩት ማብራሪያ የተወሰዱ ጥቅሶች ናቸው።
የትኛው ንግግር የየትኛው ፓርቲ እንደሆነ ለመለየት ተቸግረን ብሳሳትና ብትሳሳቱ አይገርምም። ሃሳባቸው ይመሳሰላል። ሃብት ለሁሉም በፍትሃዊነት የሚዳረስበትን መንገድ በመፍጠር እንሰራለን በማለት የቀሰቅሱ ተከራካሪ፤ ፓርቲያችን የሚከተለው አስተሳሰብ፣ “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ያለበት ፈጣንና ተከታታይ እድገትን ያመጣል” በማለት ገልፀዋል። ለዚህም በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ... በነገራችን ላይ፣ ይሄ የሌላ ተከራካሪ አባባል መሆኑን ልብ በሉ - የሦስተኛው ተከራካሪ አባባል ነው። እንዳይደባለቅባችሁ ሰጋሁ። አንዳች ማስጠንቀቂያ ምልክት ሳልሰጥ፣ ከሁለተኛው ተከራካሪ ወደ ሦስተኛው ተከራካሪ መሻገር አልነበረብኝም። ለማንኛውም፤ የኢህአዴግ ተወካይ አቶ አባይ ፀሐዬ የተናገሩትን ነው የጠቀስኩላችሁ።


Published in ዜና

     በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ 400 ያህል ሆቴሎች ደረጃ ሊሰጥ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር አስታወቁ፡፡ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አሚን አብዱልቃድር ሰሞኑን በአክሱም ሆቴል የተጀመረውንና ለአንድ ወር የሚቆየውን ሥልጠና በከፈቱበት ወቅት፣ ግማሽ ያህሉ ሆቴሎች (ከ150 እስከ 200) የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ስለሆነ፣ በመጀመሪያው ዙር የእነዚህ ሆቴሎች ደረጃ ይገለጻል ብለዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች፣ በተከታይም በሁሉም ክልሎችና መዳረሻ ቦታዎች ተፈጻሚ እንደሚሆን ታውቋል፡፡
የደረጃው አሰጣጥ በሶስት ምዕራፎች የተከፈለ መሆኑን የጠቀሱት ሚ/ሩ፤ “በመጀመሪያው ምዕራፍ ሁለት ወራት (መጋቢትና ሚያዝያ) ቅድመ ዝግጅት ይካሄዳል፡፡ ይኼውም ለባለንብረቱ፣ ለመንግስት አካላት ለፖለቲካ አመራሮች፣ … የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣል፡፡ እንዲሁም በዚሁ ጊዜ እንዴት መግባባት እንደሚቻል የኮሙኒኬሽን መመሪያ የተዘጋጀ ስለሆነ፤ ለሚዲያ፣ ለዓለም አቀፍ ተጓዦች፣ ለአስጎብኚ ድርጅቶችና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ፣ በግንቦት ወር፣ በዓለም አቀፉ የቱሪስት ድርጅት በተወከሉትና የሆቴሎችን ደረጃ በመመደብ ከ198 አገራት በላይ ልምድና እውቀት ባላቸው በሚ/ር ጀምስ የሚመራው 8 አባላት ያለው ቡድን የደረጃ ምደባውን ያካሂዳል፡፡ በሦስተኛው ምዕራፍ፣ በሰኔ ወር የምደባው ውጤት ለሆቴሎች ይነገራል” በማለት አብራርተዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጥንቃቄ የተመረጡ 52 የሆቴል ባለሙያዎች ሲሆኑ ዓላማውም ባለሙያዎች ስለሆቴል ደረጃ ምደባ፣ ሥርዓትና አፈጻጸም መረጃዎችን እንዲያገኙና የተግባር ልምምድ በማድረግ እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ መሆኑን ሚ/ሩ ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናውን የሚሰጠው በኢትዮጵያ ለሆቴሎች ደረጃ መስጠት ከተቋረጠ 12 ዓመት ስለሆነው፣ መንግሥት ዓለም አቀፍ የሆቴሎች ደረጃ መመዘኛ መስፈርት እንዲወጣ ወስኖ፣ በዓለም ያሉ ተወዳዳሪዎች እንዲሳተፉ ባወጣው ጨረታ ያሸነፈው “ዱኔራ” የተባለ ድርጅት ሲሆን ያዘጋጀውን የሆቴሎች ደረጃ መመዘኛ መስፈርት፣ የሆቴል ባለንብረቶች ማህበር፣ የቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የሆቴል ባለሙያዎች ማህበራት፣ ባለድርሻ አካላት፣ የሚ/ር መ/ቤቱ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች፣ የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች እንዲወያዩበት ተደርጎ፤ ሰነዱ፣ በኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ካውንስል የኢትዮጵያ ሆቴሎች ደረጃ መመደቢያ እንዲሆን የፀደቀ መሆኑን አቶ አሚን አስረድተዋል፡፡
ሰልጣኞቹ፣ በዚህኛው ምድብ፣ ከውጭ የመጣው ቡድን ምን እንደሚሰራና እንዴት እንደሚመድብ ከመመልከት በስተቀር በምደባው ተሳትፎ እንደሌላቸው ጠቅሰው፣ አንድ ላይ ሆነው ለ15 ቀናት ሌትና ቀን የሆቴሎች ደረጃ ምደባ፣ ትግበራና ለወደፊት ስራቸው መሰረት የሚሆናቸውን የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ሲከታተሉ፣ በቀሪው 15 ቀን ከደረጃ መዳቢዎች ጋር በየሆቴሉ በመዘዋወር የተግባር ልምምድ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
ለሆቴሎች ደረጃ ምደባ፣ ለእውቀት ሽግግርና ሥልጠና መንግስት 500ሺ ዶላር መመደቡን የጠቀሱት አቶ አሚን አብዱልቃድር፣ የሆቴሎች ደረጃ በቀጣይ ሶስት ዓመት ምን መሆን አለበት? የሚል መመሪያ (ሮድማፕ) የተዘጋጀ በመሆኑ፣ የሆቴል ባለቤቶች፣ ማናጀሮች፣ የፖለቲካ አመራሮች … የሆቴል ኢንዱስትሪውን በእውቀት እንዲመሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
አዲስ አበባ 3ኛዋ የዲፕሎማቶች መቀመጫ ናት፡፡ በየጊዜው በርካታ ቱሪስቶች ለተለያየ ጉዳዮች (ለንግድ፣ ለስብሰባ፣ ለጉብኝት…) ይመጣሉ ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረጻድቅ፤ መዲናዋ ከየትኛውም አካባቢ በላይ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ሊኖሯት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ “የሆቴሎች የደረጃ መውጣት እርስ በእርስ በሚያደርጉት ፉክክር፣ የተሻለና ጥራቱን የጠበቀ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላቸዋል፡፡ ስለዚህ ሆቴሎችን እውነተኛ ሚዛን ላይ አስቀምጦ ትክክለኛ ደረጃቸውን መንገር ያስፈልጋል፡፡ አዲስ አበባን በሆቴል አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለችና ተመራጭ በማድረግ ሆቴሎች በ2ኛው የጂዲፒ ዕቅድ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚጫወቱትን ከፍተኛ ሚና ማስቀጠል ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢ ካውንስል ካፀደቀው መመዘኛ በተቃራኒ ሆቴሎች ደረጃ ከተሰጣቸው ያልተገመተና ያልተጠበቀ ውጤት ያስከትላል” በማለት ሰልጣኞች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ ምደባ እንዲሰጡ አጥብቀው አሳስበዋል አቶ ገ/ፃድቅ፡፡

Published in ዜና

አቶ ተሻገር ሽፈራው
(በአ.አ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር)

     አድማስን ከሌሎች ጋዜጦች ለየት የሚያደርገው በርካታ ጉዳዮች አሉት፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ አጫጭር ልቦለድ ሳያቋርጥ ማስተናገዱ ሲሆን ሌላው የርዕሰ አንቀፁ ይዘትና አፃፃፍ ነው፡፡ የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀሙም ጥንቃቄ የተሞላበት መሆኑ ይሰማኛል፡፡ እየተጀመሩ መቋረጥ የአገራችን ጋዜጦች መገለጫ በሆነበት ዘመን፣ አዲስ አድማስ 15 ዓመታትን መዝለቁም ልዩ ያደርገዋል፡፡ አድማስን ማንበብ የጀመርኩት ገና ሲጀመር ነው፡፡ በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት የራሱን ማንነት (የጋዜጣ ሰብዕና) ገንብቶ ቀጥሏል፡፡ እኔ በማስተምርበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቼ ለምረቃ ጥናት ሲሰሩና አሳይመንት ስሰጣቸው አዲስ አድማስን በብዛት ይጠቀማሉ፡፡
በአጠቃላይ ጋዜጣው “አዲስ አድማስ” ተብሎ ባይፃፍበት እንኳን የሚታወቅና ለሁሉም አንባቢ የቤተሰባዊነት ቀረቤታ ያለው ሲሆን ከማነባቸው ሁለትና ሶስት ጋዜጦች ቀዳሚው ጋዜጣ ነው፡፡ በህትመት ዋጋ መናር ይመስለኛል የገፁ ብዛት እየሳሳ መጥቷል፡፡ ያም ሆኖ አድማስን ማንበብ አላቆምኩም፡፡ ለተወሰኑ አመታት እየገዛሁ አስቀምጠው ነበር፡፡ አሁንም አጓጊና ቀልብን የሚስቡ ዜናዎች ሲኖሩት እገዛዋለሁ፡፡ ቅዳሜ ቅዳሜ መግዛት የማልችልበት ቦታ ብሆን እንኳ በዌብሳይት  ሳላነብ የምቀርበት ጊዜ የለም፡፡ በሁላችንም ህሊና ውስጥ በጎ ተፅዕኖ ያሳረፈ ጋዜጣ ነው፡፡ የተዋጡና እንደ ጎደሉ የሚሰሙ አምዶችና ጸሐፍት አሉት፡፡ የቀድሞዎቹም የአሁኖቹም ግን እንደየጊዜያቸው አሪፎች ናቸው፡፡ በተረፈ ጉድለቶቹን እየሞላ፣ እያስተካከለ፣ እያገለገለን ሌሎች አስራ አምስት ዓመታትን እንዲቀጥል እመኛለሁ፡፡

Published in ዜና

ጥላሁን ጉግሣ
(የቴያትርና የፊልም ደራሲ፣ ዳይሬክተር፣
ተዋናይና የማስታወቂያ ባለሙያ)
       አዲስ አድማስ ጥሩ ጋዜጣ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ጥሩነቱ በቀለሙ ወይንም በወረቀቱ አይደለም፤ በይዘቱ ነው፤ በሚሰጣቸው መረጃዎች፡፡ በአምዶቹ አስተማሪነትና አዝናኝነት ነው፡፡ መረጃዎቹ የጋዜጠኞቹን መረጃ የመፈልፈል ብቃት የሚመሰክሩ ናቸው። አምዶቹ የተለያዩ ሰዎችን የህይወት ተሞክሮና ልምድ የምንማርባቸው ናቸው፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት በጥንካሬ ለመቆየታችሁም ሚስጥሩ ይኸው ነው፡፡ ለወደፊቱም በዚሁ እንድትቀጥሉና የተሻሉ ስራዎችን እንድታስነብቡን እመኛለሁ፡፡


Published in ዜና
Wednesday, 11 March 2015 11:42

የሂስ ጥግ

ሂስ የተወለደው ከጥበብ ማህፀን ነው፡፡
ቻርልስ ቦውድሌር
(ፈረንሳዊ ገጣሚ)
 የሚችሉ ይሰራሉ፡፡ የማይችሉ ይተቻሉ፡፡
(ምንጩ ያልታወቀ)
አንተ እንደምትፈልግ ፃፈው፡፡ ሃያሲ እንዴት የተሻለ ልትፅፈው ትችል እንደነበር ለዓለም ያስረዳልሃል፡፡
ኦሊቨር ጎልድስሚዝ
(አየርላንዳዊ ፀሃፊ፣ ገጣሚና ሃኪም)
ለሃያሲ ስንዝር ከሰጠኸው ቲያትር ይፅፋል፡፡
ጆን ስቴይንቤክ
(አሜሪካዊ ፀሐፊ)
ምላስህ የተሳለ ከሆነ ጉሮሮህን ይቆርጠዋል፡፡
(ምንጩ ያልታወቀ)
ከትችት ለማምለጥ፡- ምንም አትስራ፡፡ ምንም አትናገር፡፡ ምንም አትሁን፡፡
ኢልበርት ሁባርድ
(አሜሪካዊ አርታኢ፣ አሳታሚ እና ደራሲ)
ከባልንጀራህ ግንባር ላይ ዝንብ ለማባረር ፋስ አትጠቀም፡፡
የቻይናውያን አባባል
የሂስ ጥንካሬው ያለው በሚተቸው ነገር ድክመት ላይ ነው፡፡
ሔነሪ ዋድስዎርዝ ሎንግፌሎው
(አሜሪካዊ ገጣሚ)

Published in የግጥም ጥግ
Wednesday, 11 March 2015 11:40

የየአገሩ አባባል

ሰውን ማወቅ ከፈለግህ ሥልጣን ስጠው፡፡
የዩጎዝላቭያ አባባል
 ከመገፋትህ በፊት አትውደቅ፡፡
የእንግሊዞች አባባል
ራስህን በወዳጆችህ እንጂ በአጥር አትከልል፡
የቼክ አባባል
ውሃውን ስትጠጣ. ምንጩን አስታውስ፡፡
የቻይናውያን አባባል
 ከፊትህ የሚጠብቅህን መንገድ ለማወቅ ተመላሾቹን ጠይቅ፡፡
የቻይናውያን አባባል
አንዲት ደግ ቃል ሦስት ክረምት ታሞቃለች፡
የጃፓናውያን አባባል
እሾህ ከበተንክ ባዶ እግርህን አትሂድ፡፡
የጣሊያናውያን አባባል
ለልጅ ጦር አትስጠው፡፡
የላቲኖች አባባል
በዓይንህ ያላየኸውን በምላስህ አትፍጠር፡፡
የይሁዳውያን አባባል
 እባብ ለመያዝ የጠላትህን እጅ ተጠቀም፡፡
የፐርሻውያን አባባል
ጓደኛህ ቤት መሄድ ካላዘወተርክ፤ መንገዱን አረም ይውጠዋል፡፡
የስካንዲናቪያን አባባል
ወሬ ገዝተህ፣ ዜና ሽጥ፡፡
የዎል ስትሪት አባባል

Published in ጥበብ
Wednesday, 11 March 2015 11:37

የፀሐፍት ጥግ

እውነት ሱሪዋን የማጥለቅ ዕድል ከማግኘቷ በፊት ውሸት የዓለምን ግማሽ ታካልላለች፡፡
ሰር ዊንስተን ቸርችል
ሁለቱንም ካልቻልክ ከምትወደድ ይልቅ ብትፈራ ይሻላል፡፡
ኒኮል ማኪያቬሊ
በስራዬ ዘላለማዊነት መቀዳጀት አልፈልግም፡፡ ዘላለማዊነትን የምሻው ባለመሞት ነው፡፡
ውዲ አለን
በየቀኑ “ፎርብስ” የሚያወጣውን የባለፀጎች ዝርዝር እመለከታለሁ፡፡ እዚያ ውስጥ ከሌለሁ ወደ ስራ እሄዳለሁ፡፡
ሮበርት ኦርበን
አማልክቶቹም ቀልድ ይወዳሉ፡፡
አሪስቶትል
ወዳጆች ሊመጡና ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ጠላቶች ግን ይከማቻሉ፡፡
ቶማስ ጆንስ
ስለሙዚቃ ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ በእኔ ሙያ ይሄን ማወቅ አይጠበቅባችሁም፡፡
ኤልቪስ ፕሪስሊ
(ሙዚቀኛ)
ሴቶች ባይኖሩ ኖሮ በዓለም ላይ ያለው ገንዘብ ሁሉ ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር፡፡
አሪስቶትል ኦናሲስ
በንግግሬ ብዙ ጊዜ ተፀፅቻለሁ፡፡ በዝምታዬ ግን ፈፅሞ ተፀፅቼ አላውቅም፡፡
ዜኖክራትስ
በጓደኝነት ላይ ከተመሰረተ ቢዝነስ ይልቅ በቢዝነስ ላይ የተመሰረተ ጓደኝነት ይሻላል፡፡
ጆን ዲ.ሮክፌፉለር
በህይወት ውስጥ የተለመዱ ነገሮችን ባልተለመደ መንገድ ስታከናውን የዓለምን ቀልብ ትቆጣጠራለህ፡፡
ጆርጅ ዋሺንግተን ካርቨር
ጠላትህ ስህተት ሲፈፅም አታቋርጠው፡፡
ናፖሊዮን ቦናፓርቴ

Published in ጥበብ
Wednesday, 11 March 2015 11:34

የሲኒማ ጥግ

ኮሜዲ ለመስራት የሚያስፈልገኝ አንድ መናፈሻ፣ አንድ ፖሊስና አንዲት ኮረዳ ብቻ ነው፡፡
ቻርሊ ቻፕሊን
ተዋናይ ዓለምን በእጁ መዳፍ ላይ መፍጠር መቻል አለበት፡፡
ሎውረንስ ኦሊቪየር
 ገንዘብ መስራት አልፈልግም፡፡ እኔ የምፈልገው ታላቅ መሆንን ብቻ ነው፡፡
ማርሊን ሞንሮ
የራሱን ፊልም መመልከት አልወድም - እንቅልፍ ያመጣብኛል፡፡
ሮበርት ዴ ኒሮ
 በሙያ ዘመኔ በተወንኳቸው ገፀ ባህሪያት አማካኝነት ራሴን ለመለወጥ ሞክሬአለሁ፡፡
ቻርሊዝ ቴሮን
ትወና ከባድ አይደለም፡፡ የፊልም ፅሁፉን ታነበዋለህ፡፡ የተሰጠህን ገፀ ባህርይ ከወደድከውና ገንዘቡ አጥጋቢ ከሆነ ትሰራዋለህ፡፡ … ዳይሬክተሩ አድርግ የሚልህን ታደርጋለህ .. ስትጨርስ እረፍት ትወስድና ወደ ሚቀጥለው ስራ ትገባለህ፡፡ በቃ ይኼው ነው፡፡
ሮበርት ሚትቻም
በምትተውናቸው ገፀ ባህሪያት ውስጥ ህይወትህን መኖር ትችላለህ፡፡
ቻርሊዝ ቴሮን
በእኔ ስራ ላይ የሚፃፉ ሂሶችን አላነብም፡፡ ሁሌም በሰራሁት ኩራት ይሰማኛል፡፡
ኒኮል ኪድማን
ለፊልም ትጋት የሚጠይቅ ስራ ነው፡፡ ህዝቡ ያንን አይገነዘብም፡፡ ሃያሲያን ያንን አያዩም፡፡ ግን ብዙ ልፋት የሚጠይቅ ስራ ነው፡፡
ሮበርት ዴ ኒሮ
ልብ በሉ! በፊልም ውስጥ ትናንሽ ገፀ ባህሪያት የሉም፤ ትናንሽ ተዋንያን እንጂ፡፡
ኮንስታንቲን ስታኒስላቭስኪ
ሙያ የሚወለደው በአደባባይ ነው፤ ተሰጥኦ በግል፡፡
ማርሊን ሞንሮ

Published in ጥበብ

     ባለፉት ጥቂት አመታት የአማርኛ ፊልሞች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረና በዘርፉም የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን እያደገ መጥቷል፡፡ የፊልም ስራ አዋጪ መሆኑ የገባቸው አያሌዎችም የኖሩበትን ስራ ትተው ወደ ዘርፉ ተቀላቅለዋል፡፡
በፊልም ኢንዱስትሪው የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ሲሆን ዛሬ አንድ ፊልም በሚሊዮን ብሮች ለመሸጥ በቅቷል፡፡ ለምሣሌ “ህይወቴ” የተሰኘው ፊልም በ1.2 ሚ ብር እንደተሸጠ ታውቋል፡፡ ለፊልም ተዋናዮችና ለፊልም ስክሪፕት የሚከፈለው ገንዘብም በከፍተኛ መጠን እንደጨመረ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ዘርፉ እድገት ያሳየው በየዓመቱ በሚወጡ ፊልሞች ብዛት እንጂ ጥራት አይደለም፡፡
ከሶስት እና አራት ሳምንት በላይ በስክሪን ላይ የማይቆዩ አንዳንድ የአማርኛ ፊልሞች ገና “በዳዴ ላይ የሚገኘውን የፊልም ኢንዱስትሪ ወደ ኋላ እየጎተቱት ነው ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ አንጋፋው የፊልም ባለሙያና ምሁር ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ  የኢትዮጵያን የሲኒማ ዕድገት በተመለከተ ተጠይቀው በሰጡት መልስ፤ “በመጀመሪያ አሁን የሚሰሩት ቪዲዮዎች ናቸው እንጂ ፊልሞች አይደሉም፤ በአንዲት ቅንጣት ሁነት ላይ ተመስርተው የሚሰሩ “ሲት ኮሞች” ናቸው፡፡ እናም ሲኒማና ቪዲዮን አትቀላቅሉ፡፡ ሁለቱ ፍፁም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እዚህ ፊልም ሰራሁ ይልና ቲያትሩን በክሎዝ አፕ (በቅርብ እይታ) ያሳያል፡፡ በቃ ይሄ ሲኒማ ነው ይላል፡፡ ሲኒማ እኮ እውነታዊ ምትሃት ነው፤ እያታለለ የሚያዝናናህ። ለእኔ ዛሬ ዛሬ ከሚሰሩ ሲኒማዎች ይልቅ የቀደምቶቹ ለሲኒማ እጅግ የቀረቡ ናቸው፡፡ እነ “ጉማ”፣ እነ “ሂሩት አባቷ ማነው?” እነ “አስቴር”… ከአፍሪካ ሲኒማ ጋር ሲታዩ የሚኖሩ ፊልሞች ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው የፊልምና ትያትር ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር ኃይማኖት ዓለሙም የኃይሌ ገሪማን ሃሳብ የሚጋራ አስተያየት ሰጥቶ ነበር፡፡ “እውነቱን ለመናገር የአገራችን የፊልም ስራ ሲጀመር ከነበረበት ደረጃ ማደግና መሻሻል ሲገባው፣ እንደ ካሮት ተክል ቁልቁል እያደገ የሄደ ይመስለኛል፡፡ ሙያውን ድንገት በርካቶች ያለ እውቀትና ያለ ልምድ ገብተውበት አራክሰውታል፡፡ ዛሬ በፊልም ስራ ላይ ተሰማርተናል የሚሉ ሰዎች ቆም ብለው የሰሯቸውን ስራዎች ቢመለከቱ እነሱ ራሳቸው “ምን ነክቶን ነው?” የሚሉ ይመስለኛል፡፡ ሲኒማ ከባለሙያው ይልቅ በተመልካችና በፕሮሞተሮች እየተመራ ነው፤ ይህ ነገር መቋጫ ሊኖረው ይገባል”
የብሉ ናይል የፊልም ማሰልጠኛ አካዳሚ ባለቤት ሲኒማቶግራፈር አብርሃም ኃይሌ ብሩ በበኩሉ፤ የአገሪቱ የፊልም ኢንዱስትሪ ማደግና መጠንከር ባለበት ደረጃ ባይሆንም፣ መሞከሩ በራሱ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የሲኒማ ሙያ በቂ ዕውቀትና ልምድን ይጠይቃል የሚለው ሲኒማቶግራፈሩ፤ ትምህርቱ በትምህርት ቤት በሚገኝ ዕውቀት ብቻ የሚወሰን አለመሆኑን ገልጿልበ - በሙያው የዳበረ ዕውቀትና ልምድ ካላቸው ሙያተኞች ጋር አብሮ በመስራት፣ ደጋግሞ በመሞከርና ጊዜ በመውሰድ ራስን ማሻሻል እንደሚቻል በመጠቆም፡፡
“በውጪ አገር አንድ ሰው የራሱን ፊልም ለመስራት ከስምንት እስከ አስራ ሁለት ዓመት ሊፈጅበት ይችላል። ትምህርቱን ጨርሶ ሲወጣ ሦስተኛ ረዳት ሆኖ ነው ስራ የሚጀምረው፡፡ ቀስ እያለ ልምዱን እያዳበረ ሲመጣ ረዳት ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ዋና ሆኖ የራሱን ስራ የሚሰራው፡፡ እዚህ የሚታየው ግን ከዚህ የተለየ ነገር ነው፡፡ ሁልጊዜ አዳዲስ ሰዎች ወደ ስራው ሲገቡ ታያለሽ። “ደጋግሜ ሰርቻለሁ” የሚልሽም ቢሆን ካለፈው ስራው የተማረው ነገር አይታይም፤ ስራዎቹ ይነግሩሻል፡፡ ተመልካቹ ራሱ እኮ መልስ ይሰጣል፡፡ “የፊልሙን ጅማሬ ሳየው መጨረሻውን መናገር እችላለሁ” ይልሻል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተመልካቹ ወደ ሲኒማ አዳራሹ የሚመጣው የእውነት ፊልም ልይ ብሎ ነው ወይንስ ሌሎች አማራጭ መዝናኛዎች በማጣት አሊያም ጊዜ ለማሳለፍ ፈልጎ ነው?” ያስብልሻል፡፡ እናም መሞከሩ ጥሩ ነገር ሆኖ መሻሻልና መጠንከሩ ላይ ግን ብዙ የሚቀረው ነገር አለ፡፡” ብሏል - የፊልም ባለሙያው፡፡
በበርካታ የአማርኛ ፊልሞች ላይ በዳይሬክተርነትና ፕሮዱዩሰርነት በመስራት የሚታወቀው ዮናስ ብርሃነ መዋ፤ የአገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ዕድገት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ይናገራል፡፡ ዘርፉ የራሱ ደካማ ጎኖች እንዳሉት ግን አልሸሸገም፡፡ የሲኒማ ስራ ወደ ጥሩ አቅጣጫ እየሄደና የራሱን አብዮት እየፈጠረ ነው ያለው ዳይሬክተሩ፤ በየጊዜው ግሩም ባለሙያዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን ይናገራል፡፡
“ከካሜራ ፊትም ሆነ ከካሜራ ኋላ  መስራት የሚችሉ ጥሩ ጥሩ ልጆች እየመጡ ናቸው፡፡ እነ ሄኖክ አየለ፣ እነ ይድነቃቸው ሹመቴ፣ እነ አብይ ፈንቴ፣ እነ ቅድስት ይልማና ሄርሞን ኃይላይን የመሳሰሉ ዳይሬክተሮችን እንዲሁም እነ ሚካኤል ሚሊዮን፣ ግሩም ኤርሚያስና ሳምሶን ቤቢን የመሳሰሉ የፊልም ተዋንያኖችን እያየን ነው” ብሏል፡፡ የዚያኑ ያህልም ፊልሞች በብዛት እየተሰሩ ነው፤ ከ2004 ጀምሮ በየዓመቱ የሚወጡ ፊልሞች ቁጥር ጨምሯል፤ ከ120 ፊልሞች በላይ ለእይታ ይበቃሉ። ይህ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው” ሲል ዘርፉ ተስፋ ሰጪ እየሆነ መምጣቱን ይገልፃል፡፡ ሙያው በትምህርት መደገፍ እንዳለበት ግን ይናገራል፡፡ ጥቅሙንም ሲያስረዳ፤ “የትምህርቱ መኖር ያለአግባብ የሚወጣውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ በእጅጉ ይቀንስልናል” ብሏል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፊልም ስራ ውስጥ ስሙ እየገነነ የመጣው ወጣቱ የፊልም ባለሙያ ይድነቃቸው ሹመቴ በበኩሉ፤ በሲኒማ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየታየ ያለው መነቃቃት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁሞ፤ በሚወጡት ፊልሞች የጥራት ደረጃ ላይ ተገድ ቅሬታውን ገልጿል፡፡
ቴክኖሎጂ የሚያመጣቸው አዳዲስ ነገሮች በአነስተኛ ወጪ የተሻሉ ነገሮችን ለመስራት እንድንችል ቢያደርጉንም እኛ ግን ልንጠቀምባቸው አልቻልንም ብሏል፡፡ “ፊልሞች በብዛት የሚወጡትን ያህል ጥራት ያለው ስራ ተሰርቷል ማለት አይቻልም፡፡
ሁልጊዜም ከሚወጡ አዳዲስ ፊልሞች ጋር የሚመጡት አዳዲስ ልጆች ናቸው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሳቸውን እያሻሻሉ የሚመጡ ሰዎች አይታዩም” ያለው ይድነቃቸው ሹመቴ፤ “ፊልም እየተደጋገመ በተሰራ ቁጥር በራሱ የሚጨምረውና የሚያሳድገው ነገር አለ። ስለዚህም ከቀድሞ ስራዎቻችን እየተማርን የተሻሉ ነገሮችን ሰርተን ለተመልካች ማቅረብ ይገባናል” በማለት ሃሳቡን ሰንዝሯል፡፡
የፊልም ሙያ ስልጠናና ትምህርትን አስመልክቶ ሲናገርም፡- “ሙያውን ለማሳደግ የትምህርትና ስልጠና ጉዳይ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ሆኖም በአገራችን የሚገኙት የፊልም ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት እጅግ አነስተኛ ናቸው፤ በቂ አይደሉም፡፡ ትምህርቱና ስልጠናው በበቂ ሁኔታ ቢኖር በትምህርት የታነጸና ታሪኮቹን በብቃት መናገር የሚችል አቅም ያለው ባለሙያ ማፍራት ይቻል ነበር ብሏል፡፡ ከትምህርት ሌላ በሙያው በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች፤ ለአዳዲሶቹ ዕውቀታቸውን ማካፈልና መንገዱን ማሳየት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ ይናገራል፡፡
የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲዩሰሮች ማህበር ምክትል ሊቀመንበርና የ”ስርየት” እና “ፔንዱለም” ፊልሞች ፕሮዱዩሰር እንዲሁም የቶም ቪዲዮ ማሰልጠኛ ባለቤት ቶማስ ጌታቸው፤ የአገሪቱ የሲኒማ እድገትን በሁለት ደረጃ ከፍሎ ማየት ይገባል ይላል፡፡ ኢንዱስትሪው ገና አዲስና ወጣት ከመሆኑ አንፃር ብዙ ፊልሞች በማውጣት እንዲሁም በድምፅና በምስል ጥራት ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለፀው ባለሙያው፤ ከጭብጥ አንፃር ግን ብዙ እንደሚቀረው ጠቁሟል፡፡
“ፊልሞቻችን ከታሪክና ከጭብጥ አንፃር ብዙ ጉድለቶችና ድክመቶች አሉባቸው፤ አንዳንድ ጊዜ እንደውም፣ እየባሰበትና ወደ ኋላ እየተጎተተ ነው እንዴ? የሚያሰኙ ስራዎችን እያየን ነው፡፡ በዓመት ከሚወጡት ከ100 በላይ ፊልሞች አምስት በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸውበ የተሻሉ የሚባሉ” ብሏል፡፡
የፊልም ኢንዱስትሪው ሌላ ማነቆ በቂ የሲኒማ ማሳያ አዳራሾች አለመኖር ነው የሚሉት ባለሙያዎቹ፤ ያሉትም ቢሆኑ ከተመልካቾች ምቾትና ከድምፅ ጥራት አንፃር ደረጃቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑ ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ሥር በሚተዳደሩት ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሲኒማ አምፔርና ሲኒማ አምባሳደር ፊልሞችን አስገብቶ ለማሳየት ቢያንስ አንድ ዓመት ወረፋ መጠበቅ ያስፈልጋል ሲሉ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያስረዳሉ፡፡
አለም ሲኒማ በግል ሲኒማ ቤት ዘርፍ ግንባር ቀደም ሲሆን፤ ከዚያም ኤድናሞል፣ ሴባስቶፖል፣ አጐና፣ ፍፁም፣ ጣሊያን ት/ቤት ሲኒማ፣ ዮፍታሔ፣ ዋፋ፣ አቤልና አዶት ሲኒማ ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡  
ብዙዎቹ የፊልም ባለሙያዎች በእነዚህ የግል ሲኒማ ቤቶች ፊልም ማሳየት ውጣ ውረድ የበዛበትና በፈተና የተሞላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ፊልሞቹ በምን መስፈርት እንደሚመረጡ ግልፅ መመዘኛ የሌለበት፣ ሲኒማው መመረጥ ያልቻለበት ምክንያት የማይታወቅበት፣ ግልፅነት የሌለው አሰራር የተንሰራፋበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንድ በሲኒማ አዳራሽ ውስጥ የተቀመጠ ፊልም መዛኝ “ይህንን አክተር ቀይረው፡፡
እስከ ማለት የሚደርስ ድፍረት አለው፡፡ ይህ በጣም ስህተት ነው፡፡ ሲኒማ አዳራሾች ትርፍን ማዕከል አድርገው የተሰሩ በመሆናቸው ገበያ የሚያስገኝላቸውን ነገር መምረጣቸው ተገቢ ቢሆንም ፊልም ሰሪውንም ሆነ ተመልካቹን እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ ለመውሰድ መሞከራቸው ትክክል አይደለም” በማለት ይህም ለዘርፉ ዕድገት ማሽቆልቆል የራሱ የሆነ ትልቅ ሚና እንዳለው ይገልፃሉ፡፡
የፊልም ሽልማቶችና ፌስቲቫሎች የሲኒማውን ኢንዱስትሪ ለመደገፍና ዘርፉን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ አስተዋጽኦዋቸው የላቀ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ እነዚህ ሽልማቶችና በየጊዜው የሚዘጋጁ የፊልም ፌስቲቫሎች የውድድር መንፈስ በመፍጠር ባለሙያዎችን ለተሻለ ሥራ ያነቃቃሉ፡፡
በዚህ ረገድ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሳይቋረጥ የተካሄደው “የኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ የፊልም ፌስቲቫል” በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ሁለተኛ ዙር የሽልማት ሥነስርዓቱን በቅርቡ ያካሄደው “ጉማ አዋርድ”ም እንደአጀማመሩ ከዘለቀ ለኢንዱስትሪው ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይቀርም፡፡

Published in ጥበብ

ስዉር-ስፌት ቁጥር 2”  ሲነበብ

“... በጣም ግጥምን እየኖርከዉ፥ እየኖርከዉ ስትሄድ እንደ መመሪያ ማስቀመጥ ትችላለህ። ለምሣሌ ግጥም የግድ ቤት መምታት የለበትም የሚል? ላይ ልትደርስ ትችላለህ። ኖረህ ኖረህ ነዉ እዚህ የደረስከዉ። ታች ያለዉ ግን “ት” እና “ት” ፥ “ስ” እና “ስ” የሚጠብቀዉ ሰዉ “እህ! አሁን ገጠምኩ ሊል ነዉ እንዴ ይሄ ሰዉዬ?” ሊልህ ይችላል። እዚህ ጋ ማስረዳት ሊገባህ ነዉ። ረቂቅ ሀሳብ የሚባለዉ ነገር ረቂቅ ህብረተሰብም ይፈልጋል። ... ግጥም በብዛት ጥልቅ ስሜት፥ በመጠኑ ቴክኒክ ነዉ። ስሜትህ በጣም እየበዛ ሲሄድ በቀላሉ ትገጥማለህ። ትምህርት በጣም እየበዛ ሲሄድ ደግሞ መግጠምም ትቀንሳለህ። ቀለሙ ስሜትህን ሊያደርቅብህ ይችላል።”
-- ነቢይ መኮንን [ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ለጦቢያ ግጥምን በጃዝ ካወያየዉ የተቀነጨበ]
“ስውር ስፌት ቁጥር 2”  ለነፃ ግጥም -በከፊል ቤት ለማይመታዉ- በአንድ ግጥሙ ብቻ ተሞከረ እንጂ ለነባር የአገጣጠም ስልት አድልቶበታል፤ እርግጥ ለገሃድ ዘለል ብሎም ለምትሀታዊ እዉነታ (magic realism) በምስልም በጭብጥም ነባሩን አወላልቆ እርቃኑን፥ አዲስም ደርቦ ነቢይ ድንበር ተሻግሯል።
= በበረሃ ጐጆ የተኛች አበባ =
በጣም ሩቅ ሩቅ የሆነ በረሀ
የፍቅረኛዬን አብረቅራቂ አይኖች ጥበቃ
በበረሀ ጐጆ ከተኛች አበባ ፊት
ቁጭ ብያለሁ።
ብዙ በዙ ጠበኩ
ሆኖም በህልም አገር እንደሚኖር ሰዉ ሆንኩ።
ፍቅረኛዬ ምን ነካትና ቀረች?
እኔን ምን ዋጠኝ?
የአበባይቱስ መጨረሻ ምን ሆነ?
ይህንን የሚያዉቀዉ፥
ዐይኑን በግማሽ የጨፈነዉ፥
የአበባዋ ማስቀመጫ ብቻ ነዉ።
[ገፅ 49]
“በህልም አገር እንደሚኖር ሰዉ” ማዶ ከተንሰራፋ በረሀ የፍቅረኛዉን ማራኪ አይኖች ለመሳለም አሰፈሰፈ ... ትቀራለች፤ ግራ ይጋባል። ከሥነልቦናዊ መዘዙ ይልቅ፥ የተጠለለች አበባ ዕጣ ፈንታ የሚቀል መሰለ። “ዐይኑን በግማሽ የጨፈነዉ” የአበባ ማስቀመጫ ተምሣሌቱ የመንፈስ፥ የግዑዝ ወይስ እስከ ቅዠት የመልለጠጥ ዳበሳ ነዉ? የመጀመሪያ ስንኞች ከጫፍ የተለመደዉ ምት ተገጣጥቦ “ቀ” ሆሄ በዉስጠ-ምት እየተንቃቃ ይደመጣል፤ አይጐረብጥም። “ነ” ብቻዉን የአበባይቱን መጠዉልግ አልያም መፍካት የነዘረበትን ስንኝ ተሸክሞ ጥያቄ ምልክት መናጠቅ ጀመረ እንጂ ለመቋጫዉ ምት አልተስለመለመም። ምስጢሩ እንደ ተሸሸገ ያደፍጣል። ነቢይ ይህን ግጥም በእንግሊዘኛም ተቀኝቶበታል። የተበረከተዉ ለ“ተዋጥንበት ብዥታ” መሆኑ የግጥሙን አሻሚነት ያባብሰዋል።
“ይሁዳ ለምን አበደ?” በሚለዉ ግጥሙ [ገፅ 22፟-23] በጥቂት ስንኞች ዐይን የተላመደዉን መስመር ዜማዉን አጠንፍፎ ሲጐማምደዉ ጭብጡን ማለትም የእኛነት መማሰል፥ መደፍረስ እየቆየ መገጣጠቡን አጐላበት።
እጁን ወደ ገበታዉ፥ ከንፁህ እኩል የሰደደ
ወድቆ፥
እግር ስሞ፥
ጠቁሞ፥
ያመነበትን የካደ፥
ከዚያም ስቆ ተሳልቆ፥ ወደ ራሱ ቀን የሄደ፥
ታድያ!
ይሁዳ ለምን አበደ፥ የልቡን ካረገ ወድያ?
ያረገዉን ከወደደ
ይሁዳ ለምን አበደ?
አንድን ገፅ ትክ ብለዉ ቢያስተዉሉት በባዶ ሥፍራ እና ፊደላት በቀቡት መስመር መካከል የቀለማት ጥበት-ስፋት ለዐይንም ለልቡና የሆነ ዉበት ሲላጥ ሲሸሸግ፣ ለግጥሙም ጥልቀት የሚያክለዉ አያጣም። ስንኝ በአንድ ቃል ተኮማትሮ፥ በአንድ ሀረግ ሰክኖ፥ ቃላት ተጠራርተዉ ሲንሰራፋ ለይሁዳ ጉዞና አወዳደቅ ብሎም ለዘመነኛ ሰዉ መወናበድ፥ ከአንድ አቅጣጫ አለመርጋት ተስተጋብቶበታል። “ያመነበትን የካደ/  ከዚያም ስቆ ተሳልቆ፥ ወደ ራሱ ቀን የሄደ”ይመዘምዛል፤ ወደ ራስ ቀን መሄድ እምቅነቱ ጠብ ሊጭር ይችላል። ጌታን በሰላሳ ብር የሸጠዉን ችላ ብለን፥ አሁን ከመንደራችን ክህደቱን ወርሰዉ ዉስጣችን የታኘከላቸዉ ግለሰቦች ወደ የማን ቀን ነዉ፥ ትናንትን እየገላመጡ የሚዋከቡት? ቀን ወጣለት ነዉ ቀኑ ተናደበት? ይሁዳ አበደ ወይስ አሳበዱት? ሌላ እሾሃማ ጥያቄ ይጐነቁላል፤ ይህ እሳቦት -ከንፁህ እኩል እጅን ወደ ገበታ መስደድ- ለምን ተሸናፊዎችን ከለዘብነዉም ለህሊናቸዉ ያደሩትን መዘመዛቸዉ? ነቢይ ይህን ግጥም ያበረከተዉ “ፋሲካና ጊዜን ወደፊት ማዞር” ለሚሹ ስለሆነ ምን ማለቱ ነዉ? እንዴት አበርክቶቱ ግጥሙን ለማደናገዝ ተንሰራራ?
ነቢይ ለጊዜ የተቀኘዉን ከየግጥሞቹ ስንኞች ጀርባና ጓዳ አባብለን አንድ ወረቀት ቢሰራበት ቋንቋዉም፥ ዜማዉም፥ ኅብሩና እሳቦቱ ባስደመመን። እዉቅ አሜሪካዊ የልቦለድ ደራሲና ኖቤል ተሸላሚ Faulkner እንዳለዉ፤ ጠቅላላ ችግሮቻችንን ማሸነፍ ብንችል፥ ጊዜ ብቸኛዉ ችግራችን ሆኖ ይቀራል፤ ነቢይ መኮንን ይበልጥ ያሰጋዉ ጊዜ በተራው ሲሸነፍ፥ ሲጠወልግ ለህልፈቱ የህይወትን አፍንጫ ማሽተቱ ነዉ። “ጊዜም ቀን ይጐልበታል” [ገፅ 52] የመሰለ ግጥም ፎክነርን ሊረብሸዉ ይችላል።
የሚገርመዉ
ጊዜም እኮ እንደ ሰዉ ፊት
ሲያረጅ ይጨማደድና
ገፁን ማድያት ይወረዋል።
በሙሉና በስብርብር የዘመነኛ ሰዉ ገፅታና እንቆቅልሽነቱ የተመሰጠበት ግጥም ጭራሽ እንደ ግለሰብ ጊዜም ቀን ሲጐድልበት መፅናናት ነዉ ተስፋ መቁረጥ? ሎሬት ፀጋዬ በ“እሳት ወይ አበባ” መቅድም “ሸክላ ሠሪ ጡቧን፥ ባለቅኔው ኪነትን ከምርጥ ቃል ህይወት ዳግመኛ ይፈጥራሉ”  ያለዉ ነቢይ ቃላትን ሲያቀጣጥል ለተረፈዉ ሙቀትና ብርሃን ዋካይ ነዉ፤ ከላይ እየተቀነጨቡ ወደ ምናባችን እንደ ጣዕም የዘመቱ ስንኞች ማጤኑ በቂ ነዉ።
አገር እኛን ያለአቅሟ አዝላ ወደ ጐልጐታ ለማድረስ ስታቃስት የሆነ መለኮታዊ ሃይል ቁብ ያልሰጠዉ ተራነት ገጣሚዉ ተቆጭቶበታል። የቆጠቆጠዉ ግን ልጆቿ ከነኩሳንኩሳችን መንቀራፈፋችን ነዉ።
ሸክሟ እንኳን እንዳይቀላት
እነሱ፥ እኛና ታሪካችን
ዉሃ እንደ ተነከረ ብሉኮ ከብደን
ከመስቀሉ አልወርድ አልናት! [ገፅ 56]
    ታሪክ -የትናንቶች ክምችት ከሆነ- የፈራረሰ ጊዜና ጣጣዉ አሁንም ገጣሚዉን ሰቅዞ ይዞታል። ግለሰብ በተወሰነ የጊዜ ቅንብብ የሚከስም ከሆነ፥ ነቢይ መኮንን ይህ ሀቅ መች ገታዉ? ዛሬን ግራና ቀኝ ገላምጦ ሞት መገቻ ሳይሆን ከባህላችን፥ ከማኅበረሰቡ እምነት ተላውሶ ነዘረ እንጂ አልሰከነም፤ መሞት ሳይሆን መቀበር ሆነ ሰቆቃዉ። “አይሳሳም ለሬሳዉ” አጭር ግጥሙ የሚመስጠን ብቻ ሳይሆን ጀማዉ እድሩን፥ ዘመዱን ወይም ወዳጁን ለማስተዛዘን -ግን የግሉን ጉዳይ እያብሰለሰለ- ለግብዐተ መሬት ሲጣደፍ ባለቅኔው ያስተዋለዉ ለዕምቅ ግጥም እርሾ ሆነዉ።
አንዲት ደቃቅ እንባ ምራቅ የምታክል
ባጣንበት ሰዓት፥
መሞት ሞኝነት ነዉ አልቃሽ በሌለበት
መቃብር ሲወደድ ሰዉ እንዴት ይሞታል
እደጅ እንደሚያድር ነገሩ ጠፍቶታል?
ጐዳና-አዳሪ ሬሳ፥ መባሉን ረስቶታል?
ስንት ያዉቃል ያልነዉ ሰዉ፥ አበሻን ምን ነካዉ?
ለነብሱ ባያዝን አይሳሳም ለሬሳዉ?! [ገፅ 45]
ይህ ለድኅረ ሞት ላደፈጠ ተምኔታዊ ቅዠት ይሁን ተስፋ ከዕምነት ስንቅ ላጠራቀመ -ሲብስበት ላግበሰበሰ- ማኅበረሰብ አሁን አሁን ሲሞት ለመቀበር ሳጥኑን ግለሰብ ከተቀማ እንደ አይነስዉር ከባዕድ ቤት ዳበሳዉ ሲሰንፍበት ተደናግሯል። ከምፀት የላቀ የዛሬነት አባዜ የፈለፈለዉ ግራ መጋባት ይኰሰኩሰናል። የተፈቀደልን ይመስል ቀን መርጠን ለመስረግ ያቆበቆበ ነፍስ አፈሩ ገለባ ሆነ ሳማ ሳይለይ፥ ገና ህይወቱ ከምትነዝረዉ እኩል በረንዳ ማደሩ እንዴት ባለቅኔው ይህን ጥልቀት ለማስገር በቃ? ነቢይ መኮንን ተላምደነዉ ከረበበብን አቧራ፥ ከደበተን እንቅልፍ ብቻዉን አፈትልኮ ቃላት እየጠዘጠዙት ጀልባዉን ያዉሰናል።
የትኛዉ የአማርኛ ገጣሚ ነዉ እራሳችን ወይም ጎረቤታችን ከድመት ደመነፍሳዊ ተግባር እያነፃፀረ በሚኮሰኩሰን፥በሚናደፍ እይታና ጥበብ ተጠምዶ የተቀኘዉ? “ወሊድና ወሲብ” [ገፅ 59] ግጥሙ ከመንደራችን የየዕለት እንቅስቃሴ ተላምደነዉ ሳይቆረቁረን ቀርቶ፥ ድሩን ካደራ በኋላ ነቢይ ብቻዉን የተብሰከሰከበት ይመስል ትዕይንቱን ከምናባችን አደፈረሰዉ። ተራ ገጣሚ ትንፋሽ አጥሮት የሚፈረከስበት ጉዳይ ነዉ።
ፍቅርና ወሲብ በድመቶች አለም
አለዉ አንዳች ነገር፥ እጅግ የሚያስደምም።
ወሲብ የሠሩ እለት፥ አይጣል ነዉ ምጣቸዉ
አገር ያዳርሳል፥ ጩኸት እሪታቸዉ።
የወሊድ ለታ ግን፥ ምጥ የለባቸዉም
እንዲት ጠብታ ድምፅ፥ ቃል አትወጣቸዉም።
የኛ ግን ሌላ ነዉ
ለፍቅርም ማማጥ ነዉ
ለአንድነት ማማጥ ነዉ
ለወሊድ ማማጥ ነዉ
ለሞትም ማማጣ ነዉ
ጣር ነዉ ጅማራችን፥ ጣር ነዉ መጨረሻዉ
“ለምንድነዉ?” አልኩኝ፥ ከድመት ያነስነዉ!!
የግል የመንደር የሀገር ምጥ መራባቱ ህሊናዉን የቆረፈደዉ ነብይ፤ የድመት ደመነፍሳዊ ተግባር አስደምሞታል፤ ከዉስጣችን ዳግም ለመፍካት በጥያቄዎች የወረዛዉ እይታ እረፍት ይነሳናል። አንዳንዴ የአካባቢያችን ጋጋታ ሆነ ስክነት ለምናቡ አልመጥን ሲል ነብይ የህልምንና የምትሀትን ድንበር ጥሶ ስለዘመነኛ የከተማ ሰዉ -urban- ትካዜ እና መቅበዝበዝ በግጥም ይንሳፈፋል። ለዕዉነታ ክስተት ከሚነዝረዉ ስንኝ፥ ገጠመኝ ከለኮሰዉ አንጓ ይልቅ ወደ አደናጋሪና የማይገለጠዉ -ineffable- ርዕዮት እየታከከ ከቋንቋ ባሻገር ኢ-ንቁ አእምሮን ለመበርበር ይቀኛል። ይህን እና ሌላ ጥበባዊ ጉዳይ በክፍል ሁለት ንባቤ እመለስበታለሁ። ለእናት ሞት አንዳንዱ ቢያንጐራጉርም ነብይ መኮንን “ህይወት” በሚል ርዕስ እጅጉን የሚመስጥ ግጥም [ገፅ 60-62] ከተቀኘዉ የተቀነጨበ ለሳምንት መቆያ፥ መደመምያ  ይሁነን።
የምድጃ ዳር ተረት ስትነግረኝ የኖረች
በወጣትነቷ ዜማ አዉራጅ ነበረች
ድምጿን በቅል ዋንጫ ስትቀዳ የኖረች።
.....................
ያቺ የቅራኔ አምባ፥ ዓለም የመሰለች
እኔ አንድ ዓመት ስኖር፥ አንድ ዓመት ረገፈች።
......................
ለካ ዕዉነት ነዉ እንጂ ሰውነት አይከብድም
ደግነት ነዉ እንጂ አካል አይመዝንም።

Published in ጥበብ
Page 12 of 21