በአስር አመት ውስጥ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ለሆኑ 800 ወንድና ሴት ተማሪዎች የነፃ ትምህርት ዕድል የሚያስገኘው የማስተር ካርድ ስኮላር ፕሮግራም ትናንት በይፋ ተጀመረ፡፡ በ100 ወጣት ወንድና ሴት ተማሪዎች የተጀመረው የነፃ ትምህርት ዕድል፤ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ  ተማሪዎች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ሆኖ ጥሩ የትምህርት ፍላጐት ያላቸውንና ጐበዝ ተማሪዎችን ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ክልሎችና ከአዲስ አበባ አስተዳደር በማሰባሰብ የነፃ ትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገው ተብሏል፡፡  
Forum for African women education (FAWE) በተባለው ድርጅት በተጀመረው የነጻ ትምህርት እድል ፕሮጀክት በአስር ዓመት ውስጥ ተጠቃሚ የሚሆኑት 800 ወጣቶች ሲሆኑ 600 ያህሉ ሴት ተማሪዎች ናቸው፡፡ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች በውጭ አገር ነጻ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ሊያጋጥማቸው እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

Published in ዜና

- ከመደበኛው 218 ሚ ዶላር መሸጫ ዋጋቸው በግማሽ ቅናሽ እንደሚሸጡ ይጠበቃል
 
ቦይንግ ኩባንያ ቀደም ባለ ሞዴል ካመረታቸው የመጨረሻዎቹ ቦይንግ 787 - 8 ድሪምላይነር አውሮፕላኖችን ውስጥ ስምንቱን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሸጥ ድርድር እያደረገ መሆኑን ብሉምበርግ ኒውስ ዘገበ፡፡
ኩባንያው አውሮፕላኖቹን ለእያንዳንዳቸው ከተመነላቸው የ218 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መደበኛ የመሸጫ ዋጋ ላይ በግማሽ ያህል ቅናሽ አድርጎ ይሸጣቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ አውሮፕላኖቹን ለመግዛት ከኩባንያው ጋር ድርድር ከጀመሩት አየር መንገዶች መካከል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሸለ ድርድር በማድረግ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መዳረሱን አስታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ አውሮፕላኖችን ከኩባንያው የገዙ ደንበኞች በዚህኛው ግዢ ላይ ለመሳተፍ አለመፈለጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው የአውሮፕላኖቹ ክብደት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑን ጋር ተያይዞ የሚሸፍኑት የበረራ ክልል ውስን መሆኑ እንደሆነ ገልጧል፡፡
ቦይንግ በሚያመርታቸው ድሪምላይነር አውሮፐሮላኖች ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው የሙከራ በረራዎች፣ የተለያዩ ቴክኒካዊና የዲዛይን ችግሮች እንዳሉባቸው መረጋገጡን ተከትሎ፣ ቦይንግ ኩባንያ በአውሮፕላኖቹ ዲዛይንና አሰራር ላይ ለውጥ ለማድረግ ተገድዶ እንደነበርም ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡፡


Published in ዜና

ፓስፖርትና ህጋዊ ሰነድ ሣይኖራቸው በህገ ወጥ መንገድ ኬንያ ውስጥ ተይዘዋል የተባሉት 101 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ፍ/ቤት ቀርበው እያንዳንዳቸው 50ሺህ የኬንያ ሽልንግ እንዲከፍሉ መክፈል ካልቻልኩ በአንድ አመት እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡
በኬንያ ታሲያ በተባለችው ግዛት ሰኞ እለት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ኢትዮጵያውያኑ በ3 ኬንያውያን ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቅናት ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት ወቅት መሆኑን ኔሽን የተሠኘው የሀገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ስደተኞቹ ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤት ቀርበው የዳኛውን የ50ሺህ ሽልንግ ቅጣት ሲሰሙና ይህን ካልከፈልኩም ለአንድ አመት በእስር ከቆዩ በኋላ ወደ ሃገራቸው ተመልሰው እንደሚላኩ በአስተርጓሚ ሲነገራቸው አምርረው ማልቀሣቸውንና አንዳንዶቹም መታመማቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ከፍርድ ውሣኔው በኋላ በምልክት ቋንቋ በፍ/ቤቱ አካባቢ የነበሩ ሰዎችን ምግብ ስጡን እያሉ ሲለምኑ እንደነበርም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያውያኑን በህገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ ነበር የተባሉት ሶስቱ ኬንያውያን ላይ ፍ/ቤቱ እያንዳንዳቸው ላይ 80ሺህ ሽልንግ ቅጣት ጥሎ ቅጣታቸውን ከፍለው ወዲያውኑ ተለቀዋል ተብሏል፡፡
በኬንያ የህገወጥ ስደተኞች መበራከት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ የተጠቆመ ሲሆን የኢትዮጵያውያን ቁጥር የላቀ ድርሻ አለው ተብሏል፡፡ በቅርቡም 11 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ህጋዊ የጉዞ ሰነዶችን ሳያሟሉ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ ሲሉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቅናት በሚል በኬንያ አድርገው ሊጓዙ ሲሞክሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑንም ተጠቁሟል፡፡  

Published in ዜና

ሁለተኛው አገር አቀፍ የህብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም - 2007 በመጪው ሳምንት እንደሚካሄድ የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንጀሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ክቢር አቶ ኡስማን ሱሩር፣ ሰሞኑን በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ “የህብረት ስራ ማህበራት ስኬቶችን በማስፋፋት ህዳሴያችንን እናፋጥናለን” በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 26 እስከ 30 በኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡
ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡና በተለያዩ ዘርፎች የተሳተፉ 240 የህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና ፌዴሬሽኖች ምርትና አገልግሎታቸውን በማቅረብ ከሸማቹ ህብረተሰብ ጋር በቀጥታ በመገናኘት የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ እርስ በርስ አንዱ የሌላውን ምርት ወይም አገልግሎት በመግዛት የገበያ እድልና የልምድ ልውውጥ ይፈጥራሉ ብለዋል፡፡
በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ጠንካራ የገበያ ትስስር ሲፈጠር ህብረተሰቡ ለህብረት ሥራ ማህበራት ያለው አመለካከት ይለወጣል ያሉት አቶ ኡስማን፣ በርካታ የማህበረሰቡ አካላት ከሚገናኙባቸው እንደዩኒቨርሲቲ፣ ማረሚያ ቤቶችና ሆስፒታሎች ያሉ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን በማቅረብ ያስተዋውቃሉ የገበያም ትስስርም ይፈጥራሉ ብለዋል፡፡
በግብርና ምርት የተሰማሩ ማህበራት በኤግዚቢሽኑ ላይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ … ያቀርባሉ፡፡ ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ የተሸጋገሩ ብዙ የህብረት ስራ ማህበራት ስላሉ፣ በምርታቸው ላይ እሴት ጨምረው፣ ለምሳሌ ዛላ በርበሬ ከመሸጥ ቅመም ጨምረው በማስፈጨት ለሱፐር ማርኬቶች የሚያቀርቡ፣ ጥሬውን ገብስ ከማቅረብ፣ ወደ ቆሎ፣ ወደ በሶ፣ ወደ ጩኮ፣ … ቀይረው ለሱፐር ማርኬቶች የሚያቀርቡና ኤክስፖርት የሚያደርጉ ማህበራት ስላሉ፣ ኤግዚቢሽኑን ሲመለከቱ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ብዥታ ይቀይራል የሚል እምነት እንዳለ ገልፀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በኤግዚቢሽኑ ዋዜማ የካቲት 25 ቀን ከ700 በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የፓናል ውይይት በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ አዳራሽ (ኢሲኤ) እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ የአገራችንን የህብረት ስራና ዓለም አቀፍ የህብረት ስራ እንቅስቃሴን መነሻ ያደረጉ የመልካም ተሞክሮ ጥናታዊ ተሞክሮ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሮ አቶ ኡስማን ሱሩር፡፡

Published in ዜና

ሜድኮ ባዩ ሜዲካል ኮሌጅ የካቲት 23 እና 24 ቀን 2007 ዓ.ም ትምህርታዊ ፌስቲቫል ያካሄዳል፡፡ “የትምህርት እድልን በተቀናጀ መንገድ ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተማሪችን ማገናኘት” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ሰኞ እና ማክሰኞ በሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ በሚካሄደው ትምርታሪ ፉስቲቫል ላይ በርካታ የውጭ ዩኒርስቲዎች ይሳተፋሉ የተባለ ሲሆነ ከነዚሀም ውስጥ የአሜሪካው ፍራንክሊን ዩኒቨርሲቲ፣ የህንዱ አፋርያ ኢንስቲትዩትት የቱርኩ ኦካን ዩኒቨርሲቲ፣ የካናዳው ብሮንስቶን አካዳሚ፣ የማሌዢያው ማሌዢያ የትምህርት ማዕከል፣ የጣሊያኑ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ፣ የኡጋንዳው ቪክቶሪያ ዩኒቨርሲቲ፣ የስዊዘርላንዱ ሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ የቆጵሮሲ ግሪኒ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ፣ የአሜሪካው ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ፣ የደቡብ አፍሪካው ጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች በርካታ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገኙበት በሜድኮ ባዩ ሜዲካል ኮሌጅ የሚዲያ አስተባባሪው አቶ ቶፊቅ ሁሱን ገልጿል፡፡
በሜድኮ ባዩ ሜዲካል ኮሌጅ አስተባባሪነተ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ትምህርታዊ ፌስቲቫል ቀጣይነት ይኖረዋል የተባለ ሲሆን የሌሎች አገሮች ዩበኒቨርሲቲዎችም በቀጣይ ፌስቲቫሉን ያዘጋጃሉ ተብሏል፡፡ የፌስቲቫሉ ዋና አላማ አለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና ተማሪዎችን በማገናኘት ልምድ ማለዋወጥና በስኮላርሺፕ ሂደት ላይ ደላሎች የሚሰሩትን አሻጥር በማስቀረት የየአገራቱ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርታቸው ብልጫ ላላቨው ተማሪዎች በቀጥታ የትምህርት እድል እንዲሰጡ ለማድረግ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በቀጣዩ ሰኞና ማክሰኞ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት እስከ 11 ሰዓት በሚካሄደው ፉስቲቫል ላይ የአገራችንም ዩኒቨርሲቲዎች ይሳተፋሉ የተባለ ሲሆን ይህ ፌስቲቫል አገራችን ኢትዮጵያ ለትምህርተ ጥራትና ተደራሽነት የምታደርገውን ጉዞ በማገዝ በእውቀት የበለፀገ ማህበረሰብን ለማፍራት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የልምድ ልውውጦች፣ የፓናል ውይይቶችና መሰል ዝግጅቶች የሚካሄዱ ሲሆን ፌስቲቫሉን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መምህራን እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በስፍራው ተገኝተው እንዲጎበኙት አስተባባሪው ሜድኮ ሜዲካል ኮሌጅ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Published in ዜና

በአዲስ አበባ ከባቡር ፕሮጀክት ጋር ተያይዘው የእግረኛ መንገድ ግንባታዎች መዘግየት ያጋጠማቸው ከባቡር የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስረ ዝርጋታ ጋር ተያይዞ በየጊዜው የዲዛይን ለውጦች በመደረጉ ነው ተባለ፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ፍቃዱ ኃይሌ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት አስፋልት ስራው ያለምንም የበጀት እጥረትና ችግር በተያዘለት ጊዜ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በእግረኛ መንገድ ላይ ለተፈጠረው መጓተት ኃላፊነቱን የሚወስደው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በባር ፕሮጀክቱ አማካይነት ለኃይል ማስተላለፊያ መሬት ውስጥ የሚቀበሩት የኤሌክትሪክ መስመሮች መጠን ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ የዲዛይን ለውጥ መደረጉን የጠቀሱት ኢ/ር ፍቃዴ ባለስልጣኑ በዚህ ምክኒያት መንገዶቹን በአግባቡ እንዳይሰራ እንቅፋት እንደተፈጠረበተ ገልፀዋል፡፡
እግረኞችን ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ በፊት ቱቦዎች ያለመደፈናቸው ጉዳይም ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

በአስር አመት ውስጥ ስምንት መቶ ወንድና ሴት አቅመ ደካማ ተማሪዎችን የነፃ ትምህርት ዕድል የሚያስገኘው የማስተር ካርድ ስኮላር ፕሮግራም ትናንት በይፋ ተጀመረ፡፡
በአንድ መቶ የኢኮኖሚ አቋማቸው ደካማ በሆኑ ወጣት ወንድና ሴት ተማሪዎች በትናንትናው ዕለት በይፋ የተጀመረው የማስተር ካርድ የነፃ ትምህርት ዕድል ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ወጣት ወንድና ሴት ተማሪዎች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ሆኖ ጥሩ የትምህርት ፍላጐት ያላቸውንና ጐበዝ የሆኑ ተማሪዎችን ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ክልሎችና ከአዲስ አበባ አስተዳደር በማሰባሰብ የነፃ ትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
Forum for African women education (FAWE) በተባለው ድርጅት ተግባራዊ በሆነው በዚሁ የፋዌ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሚሆኑት ስምንት መቶ ወጣቶች ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 600 ያህሉ ሴት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱ ለአስር አመታት የሚቆይ ሲሆን የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ሆነው በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ በትምህርታቸው ከፍ ያለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ለከፍተኛ ትምህርት ወደውጪ አገር የመሄድ የነፃ ትምህርት ዕድልም ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ተገልጿል፡፡

Published in ዜና

በግንቦቱ ምርጫ ህዝቡ በእውቀት ላይ ተመስርቶ እንዲመርጥ ያሳሰበው ኢዴፓ፣ ህብረተሰቡ የፓርቲውን አማራጭ አስተሳሰቦች ገምግሞ እንዲመርጥ የሚያስችል የመወዳደሪያ ማኒፌስቶ ማውጣቱንም አስታውቋል፡፡
ፓርቲው ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ ቢመረጥ ሊተገብራቸው የሚፈልጋቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አማራጮችን ከገዥው ፓርቲ በተለየ በግልፅ ማስቀመጡንና ለወጣቱ ትውልድም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁሟል፡፡
“የስልጣን መገኛው መንገድ ምርጫና ምርጫ ብቻ ነው” ያለው ፓርቲው፤ የግንቦቱ ምርጫ  የተሳካና ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆን የበኩሉን ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልፆ ገዥው ፓርቲም ሆነ ምርጫ ቦርድ ባላቸው ኃላፊነት ከአድሎአዊነትና ከወከባ የፀዳ የፖለቲካ ምህዳር እንዲያመቻቹ፣ ለመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት መጠናከርም ቁርጠኝነታቸውን በተግባር እንዲያረጋግጡ ጠይቋል፡፡
መራጩ ህዝብም በጭፍን ከመደገፍና  ከመቃወም ይልቅ በእውቀት ላይ ተመስርቶ አማራጭ ሃሳቦችን በመገምገም ያሻውን ፓርቲ በሰለጠነ መንገድ እንዲመርጥ ኢዴፓ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

Published in ዜና

119ኛውን የአድዋን የድል በዓል ለማክበር ጥር 15 ቀን 2007 ወደ አድዋ የእግር ጉዞ የጀመሩት ስድስቱ ተጓዦች ዛሬ “እንዳአባ ገሪማ” የሚባል ቦታ በሰላም መድረሳቸው ታውቋል፡፡
ሲሳይ ወንድሙ፤ መኮንን ሞገሴ፣ ጽዮን ወልዱ፣ ግደይ ስዩም፣ ታምሩ አሸናፊና አዳነ ከማል የተሰኙት እኒህ ተጓዣች እስካሁን በጉዟቸው ምንም ችግር እንዳልገጠማቸውና ሴቷም ተጓዥ ብትሆን በጉዞዋ ከወንዶቹ እኩል መቀጠል እንደቻለች ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡ በነገው እለት አድዋ ገብተው የሶሎዳን ተራራ ግማሽ ያህሉን ወጥተው ያድራሉ የተባሉት ተጓዦቹ ሰኞ በማለዳ ተነስተው ወደ ሶሎዳ ተራራ ጫፍ በመውጣት ባንዲራ ከሰቀሉ በኋላ ተራራውን ወርደው አድዋ ከተማ ውስጥ የሚከበረውን የአድዋ 119ኛ በዓል እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡ አምና 118ኛውን የአድዋ በዓል ለመታደም አምስት ተጓዦች ለ40 ቀናት በእግራቸው ተጉዘው አድዋ መድረሳቸው የሚታወስ ሲሆን የዘንድሮውን ጉዞ ሴት ተጓዥ መቀላቀሏ ለየት ያደርገዋል ተብሏል፡፡

Published in ዜና

ለብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪ አማራጭ እንደሆኑ በጥናት ሪፖርት ተገልጿል
በአዲስ አበባ የሚገኙ የጤና ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት በአመዛኙ በመንግስት ስር ካሉት ተቋማት የተሻለ ቢሆንም፣ ግማሽ ያህሉ ገና ከደረጃ በታች እንደሆኑ ተገለፀ፡፡ በመንግስትና በግል ጤና ተቋማት ያለው የክፍያ ልዩነት ከአራት እስከ አርባ እጥፍ ይደርሳል፡፡
የግል ህክምና ተቋማት በአዲስ አበባ የሚሰጡት አገልግሎት ላይ ጥናት የተካሄደው በ“ማህበራዊ ጥናት መድረክ” አማካኝነት ሲሆን፣ ትናንት ይፋ የሆነው የጥናት ሪፖርት ከአገልግሎት ጥራት በተጨማሪ የክፍያ መጠኖችንም በማነፃፀር ዳስሷል፡፡ የግል የጤና ተቋማቱ ከመንግስት የጤና ተቋማት ጋር ሲነጻጸሩ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የጥናት ሪፖርቱ ጠቅሶ፤ ይህ ማለት ግን የአገልግሎት ደረጃን ያሟላሉ ማለት እንዳልሆነ ገልጿል፡፡
አዳዲስ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች የስራ ፈቃድ የሚያገኙት በቅርቡ እንደ አዲስ በተዘጋጀው የጥራትና ደረጃ መስፈርት እንደሆነ በጥናቱ የተገለፀ ሲሆን በመስፈርቱ መሰረትም 34 የግል ሆስፒታሎች ላይ ዝርዝር ጥናት ተካሂዷል፡፡ የጥናቱ ሪፖርት እንደሚገልፀው፤ የጥራት ደረጃ መስፈርቶችን በአግባቡ ያሟላሉ ሆስፒታሎች ከሁለት አይበልጡም፡፡ 17 ያህል ሆስፒታሎች (ማለትም 50% ያህሉ) በመካከለኛ ሁኔታ ላይ እንደሆኑና ማሻሻያ እንደሚያስፈልጋቸው ጥናቱ ገልፆ፤ 15 ያህል ሆስፒታሎች ግን በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው ብሏል፡፡
 ባለፉት አምስት አመታት የግል የህክምና ተቋማት እድገት ማሳየታቸውን ያመለከተው ጥናቱ፤ 42 በመቶ ለሚሆነው የከተማዋ ነዋሪ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነና አገልግሎታቸው ለከተማው ሀብታሞች ብቻ ሳይሆን በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ነዋሪዎችም ጭምር እንደሚደርስ ገልጿል፡፡
ጥናቱ የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ የግል የጤና ተቋማት ከሚሰጡት የአገልግሎት ጥራት ጋር ያልተመጣጠነ ከፍተኛ ክፍያ እንደሚጠይቁ አመልክቷል፡፡ በተለይ ከመንግስት የጤና ተቋማት ጋር ሲነጻጸር ክፍያው የትየለሌ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ ለምሳሌ በኤክስሬይ የዋጋ ልዩነቱ 40 እጥፍ ገደማ ሲሆን በወሊድ አገልግሎትም በተመሳሳይ የክፍያ ልዩነቱ ወደ 40 እጥፍ ይጠጋል፡፡
በእርግጥ የግልና የመንግስት የጤና ተቋማት ክፍያ ተቀራራቢ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ የመንግስት የጤና ተቋማት ስራቸውን የሚያከናውኑት ከክፍያ በሚያገኙት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከታክስ ከሚሰበሰብ ገንዘብና ከውጭ ከሚመጣ እርዳታ በጀት እተመአበላቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡  

የአገልግሎት አይነት    የግል ሆስፒታል ክፍያ በአማካይ    የጤና ጣቢያ ክፍያ በአማካይ
የካርድ                        100           5
ኤክስሬይ                      180          35
በምጥ ማዋለድ               1940           50
በኦፕራሲዮን ማዋለድ         3550         140
የወንዶች ግርዛት                520          35
ትርፍ አንጀት ቀዶ ህክምና    2850          120
የአልጋ አንደኛ ደረጃ            850          90
የአልጋ ሶስተኛ ደረጃ           350          20

በግል የጤና ተቋማት ውስጥ እንደ ችግር ከተጠቀሱት መካከል ለባለሙያዎች ማበረታቻና ተከታታይ ስልጠና አለመሰጠቱ፣ በህክምና ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶች የመሥሪያ መሬት ለማግኘት መቸገራቸው፣ የባለሙያዎች እጥረት፣ የብድር እጦት፣ የጉምሩክ ቢሮክራሲና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይገኙባቸዋል፡፡  





Published in ዜና
Page 21 of 21