- አልቃይዳ በዋይት ሃውስ ላይ ጥቃት የመፈጸም ዕቅድ ነበረው


ኦሳማ ቢላደን በህይወት በነበሩበት ጊዜ በምዕራባውያን  አገራት የሽብር ጥቃቶችን ለመሰንዘር በተያዙ ዕቅዶች ዙሪያ ከአልቃይዳ መሪዎች ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች መገኘታቸውን  ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
ከአልቃይዳ ጋር በመተባበር በእንግሊዝ የሽብር ጥቃቶችን ለመሰንዘር አሲሯል በሚል ክስ የተመሰረተበትን አቢድ ናስር የተባለ ፓኪስታናዊ ተማሪ ጉዳይ በመመርመር ላይ የሚገኘው የኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ባለፈው ረቡዕ በዋለው ችሎት፣ ቢላደን ከቡድኑ መሪዎች ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በማስረጃነት ቀርበዋል፡፡ ደብዳቤዎቹ ቢላደን በሩስያ፣ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝና በሌሎች የምእራቡ አለም አገራት ላይ የሽብር ጥቃቶችን ለመሰንዘር ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበር ያጋለጡ ሲሆን በአቦታባድ ተደብቀውበት በነበረው ግቢ ውስጥ በአሜሪካ ወታደሮች እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ከሚኖሩ የቡድኑ የጥቃት መሪዎች ጋር የሽብር ሴራ መልዕክቶችን ይለዋወጡ እንደነበር ያረጋገጡ ናቸው ተብሏል፡፡ አልቃይዳ በዋይት ሃውስ ላይ የሽብር ጥቃት የመሰንዘር ትልቅ እቅድ እንደነበረው የሚገልጽ ደብዳቤ ከመገኘቱ በተጨማሪ፣ ቢላደን አዳዲስ የጥቃት መፈጸሚያ መንገዶችን መቀየስ እንደሚገባ ከጥቃት መሪዎቹ  ጋር ያደረጉትን ውይይት የሚጠቁሙ  ደብዳቤዎችም ተገኝተዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የ5ጂ ፍጥነት ከ4ጂ በ65ሺህ እጥፍ ይበልጣል
 - 100 ፊልሞችን በሶስት ሰከንድ ማውረድ ያስችላል

   የሱሬ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በታሪክ እጅግ ፈጣኑ የተባለለትን የ5G (የአምስተኛው ትውልድ) የኢንተርኔት መረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በጥቅም ላይ ከሚውሉት የመረጃ ልውውጦች ፍጥነት በብዙ ሺህዎች እጥፍ የላቀ ነው የተባለለት የ5ጂ ፈጠራ፣ በሰከንድ አንድ ቴራ ባይት መጠን ያለው መረጃ የማስተላለፍ አቅም ያለው ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው የ5ጂ ፈጠራ ማዕከል ሃላፊ፤ አዲሱ ቴክኖሎጂ ከሶስት አመታት በኋላ በይፋ ተጠናቅቆ ለህዝብ እይታ እንደሚበቃ የተናገሩ ሲሆን ምርምሩን የሚመራው ኦፍኮም የተባለ ኩባንያም፤ ፈጠራው እስከ 2020 ድረስ በእንግሊዝ ተጠቃሚዎች እጅ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁሟል፡፡
የቴክኖሎጂው ፍጥነት እጅግ የላቀ እንደሆነ የጠቆመው ቢቢሲ፤ የአንድ ሙሉ ፊልም መቶ እጥፍ ያህል መረጃ ያለውን ፋይል በሶስት ሰከንድ ብቻ ማውረድ (ዳውንሎድ ማድረግ) እንደሚያስችል  አስረድቷል፡፡ የ5ጂ ፍጥነት፣ በአሁኑ ሰአት ጥቅም ላይ እየዋለ ከሚገኘው 4ጂ አንጻር ሲወዳደር ከ65 ሺህ እጥፍ በላይ እንደሚበልጥም አመልክቷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ስልጣን ከያዝን ቦኮ ሃራም በናይጀሪያ አይኖርም ብለዋል

በመጪው ወር በሚካሄደው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኦል ፕሮግሬሲቭስ ኮንግረስ የተባለውን  የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ በመወከል የሚወዳደሩት የፓርቲው መሪ ሙሃሙዱ ቡሃሪ፣ ፓርቲያቸው ስልጣን ቢይዝ ቦኮ ሃራም ከተባለው አሸባሪ ቡድን ጋር ሰላማዊ ድርድር እንደማያደርግ አስታወቁ፡፡ ጽንፈኛውን ቡድን ለማጥፋት ብቸኛው አማራጭ የሃይል ጥቃት መሰንዘር ነው ያሉት ቡሃሪ፤ በስልጣን ላይ ያለው የአገሪቱ መንግስት በቡድኑ ላይ የሚያሳየውን መለሳለስ ክፉኛ ነቅፈውታል፡፡
“ቦኮ ሃራም የሰላም ፍላጎት የሌለው የጥፋት ቡድን ነው፤የሰላም ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ 13 ሺ ናይጀሪያውያንን አይገድልም ነበር” ያሉት የቀድሞው የአገሪቱ የጦር አዛዥ ሙሃሙዱ ቡሃሪ፣ ፓርቲያቸው በምርጫው አሸንፎ ስልጣን ከያዘ፣ ቦኮ ሃራም በናይጀሪያ ግዛት ውስጥ ስንዝር መሬት እንደማይኖረው አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን መንግስት፣ ሰሞኑን በአሸባሪ  ቡድኑ ላይ የተጠናከረ ዘመቻ ማወጁን ያስታወቀ  ሲሆን የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ግን  “ፍሬ ቢስ” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የገጣሚ ራሄል ተሾመ “እንካችሁ አደራ” የግጥም መድበል ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ አምስት ኪሎ ብሄራዊ ሙዚየም ጀርባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መድበሉ 65 ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን ገጣሚዋ በአገር ቤት፣ በጃፓንና በአሜሪካ ቆይታዋ ያካበተቻቸውን የህይወት ተመክሮዎች በሳቅና በቁም ነገር፣ በተግሳፅና በምክር በግጥም መልክ ለአንባብያን በአደራ መስጠቷን በማስታወሻዋ ገልፃለች፡፡ በ110 ገፆች የተቀነበበው መድበሉ፤በ30 ብር ይሸጣል፡፡
በሌላ በኩል በደራሲ እነዬ ሺበሺ የተጻፈው “ያልጠራ ደም” ረጅም ልቦለድ መፅሀፍ ነገ ጠዋት ከ3፡00 ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ይመረቃል፡፡ ዋና ጭብጡን የደም ውርስ ላይ አድርጎ በርካታ ከደም ውርስ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን የሚዳስሰው መፅሀፉ፤ የደራሲዋ ሁለተኛ ስራ ሲሆን ከዚህ ቀደም “የገቦ ፍሬ” የተሰኘ ረጅም ልቦለድ መፅሀፍ ማሳተሟ ይታወቃል፡፡ በ317 ገጾች የተቀነበበው “ያልጠራ ደም”፤ ሰሞኑን በ65 ብር ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡  
በአክመል ተማም የተዘጋጀው “ዩኒቨርሳል” የተሰኘ በሥነ ክዋክብት ምርምር ላይ የሚያጠነጥን መፅሀፍም ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መፅሀፉ በአራት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን ስለ ከዋክብት፣ሚልኪዌይ፣ ጋላክሲ፣ ፀሐይና ሌሎች ፕላኔቶች በስፋት ይዳስሳል፡፡ ቁስ አካልንና ጨረርን እንዲሁም በእነሱ የተያዘውን ቦታ ጭምር ስለሚጠቀልለው ዩኒቨርሰ የሚተነትን ሲሆን በአስትሮኖሚና አስትሮሎጂ ዙሪያ ያለውን ብዥታም ለማጥራት ይሞክራል፡፡ በ123 ገጾች የተቀነበበው መጽሃፉ፤ በ35 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

የሰዓሊ ቴዎድሮስ መስፍን (ቴዲ ማን) ከ30 በላይ የካርቱን ስዕሎች የቀረቡበት “ስዕላዊ ምፀት እና ስዕላዊ ስላቅ” የተሰኘ የስዕል ትርዒት ጥር 22 ቀን 2007 ዓ.ም በጋለሪያ ቶሞካ መከፈቱ የሚታወስ ሲሆን በነገው ዕለት ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በሥራዎቹ ላይ ውይይት ይካሄዳል፡፡
የጋለሪው አርት ዳይሬክተር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ሰዓሊያን፣ የስዕል አፍቃሪያን፣ ጋዜጠኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በውይይቱ ላይ እንደሚሳተፉ የጋለሪው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ ተናግሯል፡፡ ውይይቱ በሰዓሊው ስራዎች፣ በአሳሳል ፍልስፍናው፣ ስዕሎቹ ለአገራችን ስነ-ጥበብ ባላቸው ፋይዳና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል ተብሏል፡፡ ጋለሪያ ቶሞካ 14ኛውን የስዕል ትርዒት ከአንድ ወር በኋላ ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሆነም ታውቋል፡፡

በፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር አሳታሚነት የታተመውና በህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ ያተኮረው “ታጋቾቹ” የተሰኘ የአጫጭር እውነተኛ ታሪኮች መድበል እንዲሁም ቀደም ሲል ድርጅቱ ካሳተማቸው መጻህፍት  ተመርጠው ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎሙት “Blood Price” እና “Ditached in the Jungle” የሚሉ መጻህፍት የፊታችን ሐሙስ በሐርመኒ ሆቴል  ይመረቃሉ፡፡
መጻህፍቱ ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያና ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንደተዘጋጁ  ታውቋል፡፡ በምርቃትሥነ ስርዓቱ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት፣የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ የፕሮግራሙ አዘጋጆች አስታውቀዋል፡፡ 

የሰዓሊ ቴዎድሮስ መስፍን (ቴዲ ማን) ከ30 በላይ የካርቱን ስዕሎች የቀረቡበት “ስዕላዊ ምፀት እና ስዕላዊ ስላቅ” የተሰኘ የስዕል ትርዒት ጥር 22 ቀን 2007 ዓ.ም በጋለሪያ ቶሞካ መከፈቱ የሚታወስ ሲሆን በነገው ዕለት ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በሥራዎቹ ላይ ውይይት ይካሄዳል፡፡
የጋለሪው አርት ዳይሬክተር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ሰዓሊያን፣ የስዕል አፍቃሪያን፣ ጋዜጠኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በውይይቱ ላይ እንደሚሳተፉ የጋለሪው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ ተናግሯል፡፡ ውይይቱ በሰዓሊው ስራዎች፣ በአሳሳል ፍልስፍናው፣ ስዕሎቹ ለአገራችን ስነ-ጥበብ ባላቸው ፋይዳና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል ተብሏል፡፡ ጋለሪያ ቶሞካ 14ኛውን የስዕል ትርዒት ከአንድ ወር በኋላ ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሆነም ታውቋል፡፡

“የጥቁሮች ታሪክ ወር” ተብሎ የሚጠራውን የየካቲትን ወር ምክንያት በማድረግ በአሜሪካ ኤምባሲ ድጋፍ የተዘጋጀና በአፍሪካ አሜሪካዊ ሴት ሰዓሊያን ስራዎች ላይ ያተኮረ “የአፍሪካ አሜሪካዊ ሴቶች የስዕል ስራ ከ19-21ኛው ክፍለ ዘመን” የተሰኘ የስዕል ትርኢት ሰሞኑን በብሄራዊ ሙዚየም የተከፈተ ሲሆን በክልል ከተሞችም ይቀርባል ተብሏል፡፡ ስዕሎቹ በ1943 እ.ኤ.አ ጄምስ ቪ ሄሪንግ እና አሎንዞ ጄ ኤደን በተባሉ ሁለት አፍሪካ አሜሪካዊ ፕሮፌሰሮች በተመሰረተው “ባረንት ኤደን ኮሌክሽን” ጋለሪ ውስጥ ተቀምጠው እንደነበር የተገለፀ ሲሆን በትውልድ ጃማይካዊት በዜግነት አሜሪካዊት በሆነችው ዶ/ር ደስታ ሚግ አስተባባሪነት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለእይታ እንደበቁና አሜሪካ ኤምባሲም ዝግጅቱን ስፖንሰር እንዳደረገ ለማወቅ ተችሏል፡፡   
ባለፈው ረቡዕ ተከፍቶ በዚያኑ እለት ምሽት በተዘጋው የስዕል ትርዒት ላይ የቀረቡት 40 ስዕሎች ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት አፍሪካ አሜሪካዊያን ስላሳለፉት የባርነት ዘመን፣ የነፃነት ትግል፣ እንዲሁም ስለ ባህላቸው፣አለባበሳቸውና ማንነታቸው የሚገልጹ ናቸው ተብሏል፡፡ ስዕሎች ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ በባህር ዳር፣ በድሬደዋ፣ በሃረር እና በጅማ ለእይታ ይበቃሉ ተብሏል፡፡

የኦላፍር ኤሊያሰን የስዕል ስራዎች ለእይታ የቀረቡበት “በጊዜ ላይ ጊዜ” (Time Sensitive Activity) የስዕል አውደ ርዕይ ከትላንት በስቲያ ምሽት በስነ ጥበባት ኮሌጅ በሚገኘው የገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከል (ሞደርን አርት ሙዚየም) ውስጥ ተከፈተ፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ ሚያዝያ 7 ቀን 2007 ዓ.ም  ድረስ ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል ተብሏል፡፡ ሰዓሊው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ዲዛይነር እንደሆነም ታውቋል፡፡

Monday, 02 March 2015 10:26

እናትን ፍለጋ

የመክሰስ ሰዓት ነው፡፡
“እማ….” አለ ትንሹ እዮኤል ፈራ ተባ እያለ
“ምን ፈለግክ?” አለችው እናቱ ፊትዋን እንዳጨለመች
“ራበኝ!”
“የሚበላ ነገር የለም!”
“ማሚ…በጣም እኮ ነው የራበኝ” አለ እዮኤል፤ በልጅ አንደበቱ በፍርሃት እንደተያዘ፡፡
“አይ… እንግዲህ ነገርኩህ…ቻለው!”
እዮኤል ዝም ብሎ ዓይኑን እያቁለጨለጨ ያያት ገባ፡፡ በቆመበት ትታው ወደ ጓዳ ገባች፡፡
የሆነ የሚበላ ነገር ልትፈልግልኝ ይሆናል ብሎ አሰበ እዮኤል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ወደ ጓዳ የገባችው የሱን የረሃብ ጥያቄ ልትመልስ ሳይሆን ጉዳይዋን ለመፈፀም ነበር፡፡ የራስዋን ጉዳይ፡፡ ጉዳዩ ምንድነው? ..ምንም አያገባንም፡፡ ስለዚህ ዝም ብለን እንለፈው፡፡
ሁለቱ ወንድሞቹ መክሰሳቸውን በልተው ውጪ እየተጫወቱ ነው፡፡ ምንድነው የሚጫወቱት?
ብይ፣ ቆርኪ፣ ሰኞ ማክሰኞ፣ ሱዚ፣ ኳስ፣ …. ወይም ከእነዚህ አንዱን፡፡ ወይም ከእነዚህ ሁለቱን፡፡ ወይም…
ከትምህርት ቤት የመጡት አብረው ነው፡፡ ዩኒፎርማቸውን ቀይረው እንደጨረሱ እናቱ እሱን ወደ ሱቅ ልካው፤ ለሁለቱ ልጆችዋ የሚበሉትን አቀረበችላቸው፡፡ እዮኤል ወደ ሱቅ የተላከው ክብሪት ግዛ ተብሎ ነው፡፡ ክብሪቱ ተፈልጐ ግን አልነበረም፡፡ በርካታ ክብሪት በፓኮ ፓኮ ሆኖ ቁምሳጥን ውስጥ ተቆልፎበታል፡፡ እዮኤል ወደ ሱቅ የተላከው ዞር እንዲል ስለተፈለገ ነው፡፡ ዞር ባለበት ወንድሞቹ መክሰሳቸውን በልተው ጨረሱ፡፡ እዮኤል ባዶ ሆዱን፣ የወስፋቱን ጩኸት እያዳመጠ ክብሪቱን ይዞ ገባ፡፡ እሱ (እዩኤል) ሲገባ እነሱ (ወንድሞቹ) ወጡ!
“እማ…እማ…” አለ እዮኤል፤ ሆዱን ይዞ እየተንቆራጠጠ፡፡ ማለት የፈለገውን አላለም፡፡ ማለት የፈለገው ምን ነበር? ጠፋበት፡፡ እና ዝም አለ፡፡ እናቱ የለበሰችው ረጅም ቀሚስ ላይ ነጠላዋን ደርባ ወጣች፡፡ ወዴት እየሄደች እንደሆነ አላወቀም፡፡ ሊከተላት ከጀመረ በኋላ እግሩ ተሳስሮበት እዚያው በቆመበት ደርቆ ቀረ፡፡
ሄደች እናቱ…….
እናቱ ሄደች….
ምናልባትም የሄደችው ጓደኛዋ ኤልሳ ጋር ይሆናል፡፡ ኤልሳን አብዝቶ ይወዳታል - እዮኤል፡፡ ፍቅር ትሰጠዋለች፡፡ እናቱ የነፈገችውን ፍቅር ከእሷ ነው የሚያገኘው፡፡
እቤት ስትመጣ፤
“እዩ……” ብላ ትጠራዋለች፡፡
“አቤት!”
“ና የኔ ቆንጆ”
ፀጉሩን በፍቅር ታሻሽለታለች፡፡ ሁለት ጉንጩን፣ ግንባሩን፣ አፍንጫውን፣ አገጩን፣ አንገቱን እያፈራረቀች ትስመዋለች፡፡
“አንተም ሳመኝ…” ስትለው እሱም አፀፋውን ይመልሳል፡፡ ጉንጭዋን ፣ ግንባርዋን፣ አፍንጫዋን፣ አገጯን፣ አንገቷን እያገላበጠ ይስማታል፡፡ የእናቱ ጓደኛ ኤልሳ ከወንድሞቹ ናትናኤልና በረከት ይልቅ ለእሱ ታደላለች፡፡ ለምን እንደሆነ አያውቅም፡፡ ግን ታደላለች፡፡ ህፃኑ እዮኤል የተመስገንን ትርጉም በአግባቡ ባያውቅም “ተመስገን!” ይላል እሷን ሲያገኝ፡፡ ወይም ሲያይ ወይም ስትስመው ወይም ሲስማት፡፡ ምን እንደሆነ በማያውቀው የፍቅር ሰንሰለት ተሳስረዋል - ሁለቱ - እዮኤልና ኤልሳ፡፡
አንዳንዴ ወደ ቤትዋ ይዛው ትሄዳለች፡፡ ትሄድና ምን የመሰለ ቀይ በርበሬ እንደ ሊፒስቲክ የተቀባ፣ በቅቤ ያበደ ፍርፍር ትሰራለታለች፡፡ ትሰራለትና በዝርግ ሳህን አድርጋ ታቀርብለታለች፡፡ እዮኤል አንገቱን ደፍቶ በተመስጦ ይመገባል፡፡ እያንዳንዱን ጉርሻ እያጣጣመ፡፡ ላጣጣመው እያንዳንዱ ጉርሻ ትርጉም እየፈለገ፡፡ ፍርፍርንና የፍርፍርን ምንነት እየተነተነ፡፡ ትርጉም አለው፤ እያንዳንዱ ጉርሻ ትርጉም አለው፡፡
ኤልሳ ቤት ሲመጣ የሚበላው ፍርፍሩን ብቻ አይደለም፡፡ ፍርፍሩንም ይበላል፡፡ ግን ከፍርፍሩ በላይ የሚበላው ፍቅርን ነው፡፡ በቅቤ ከወዛው ብጥስጥስ እንጀራ ውስጥ እራሱን እያየ፤ በዕድሉ እያዘነ፡፡ ሲጐርስ እየተፅናና፡፡ አንዳንዴ አጠገቡ ቁጭ ብላ ታጐርሰዋለች፡፡ ጉርሻዋን እየተስገበገበ ይውጣል፡፡ ከመብላቱ በላይ የሚያጐርሰው ሰው መገኘቱ እየደነቀው፣ ከጉርሻው ይልቅ ከጉርሻው ጀርባ ያለው ትርጉም እየመሰጠው በልቶ ይጨርሳል፡
አሁን እናቱ ጓደኛዋ ኤልሳ ጋ ሄዳ ይሆናል ብሎ ሲያስብ ኤልሳን አስታወሰ፡፡ አስታወሰና “ምን ነው አሁን በመጣች?” አለ፡፡ ፍርፍሩ፣ ምግቡ ቀርቶ መጥታ እንዲሁ ስትስቅለት፣ ስታጫውተው፣ ስታወያየው፣ ስትዳስሰው፣ ስትስመው…፡፡ ይሄ ቢሆን አሁን የተሰማው ባዶነት ይቀንስለት ነበር፡፡ የተሰማው ቅዝቃዜ ይለቀው ነበር፡፡ አዎ! የሰው አልባነት ስሜትና የብቸኝነት ቅዝቃዜው ይለቀው ነበር፡፡
“ወደ ቤትዋ ቀጥ ብዬ ብሄድስ?” ብሎ አሰበ፡፡ አይሆንም፡፡ እናቱ እዚያ ትኖር ይሆናል፡፡ ከኖረች ደግሞ በዋዛ አትለቀውም፡፡ “አንተ ቀላዋጭ!” ብላ ትጮህበታለች፡፡
“ምን ልትቀላውጥ መጣህ?”
…ከወንድሞቹና ከሰፈሩ ልጆች ጋር ሊጫወት አስቦ ወደ ደጅ ወጣ፡፡
የሰፈሩ ማቲዎች መንደሩን ሞልተውታል፡፡ ሌሎቹን ትቶ ወንድሞቹ ወደነበሩበት ቦታ ሄደ፡፡ ጥምጥሞ እየተጫወቱ ነበር፡፡
“አለሁበት…….” አላቸው፡፡
ወንድሙ በረከትና የሰፈሩ ልጅ ፍራኦል ናቸው እየተጫወቱ ያሉት፡፡ ሌላኛው ወንድሙ ናትናኤል ቆጣሪ ነው፡፡ አንዱ ሲሸነፍ ቦታውን ለመረከብ ነቅቶ እየጠበቀ ነው፡፡
“ካንተ ቀጥዬ ቆጣሪ ነኝ” አለ እዮኤል፡፡ ተስማሙ፡፡ እነሆ የእዮኤል ተራ ደረሰ፡፡ ያሸነፈው የሰፈሩ ልጅ ፍራኦል ነው፡፡ ስለዚህ እሱን (ፍራኦልን) ሊገጥመው ነው፡፡ ጨዋታው ተጀመረ፡፡
እዮኤልና ፍራኦል ብዙ ተፎካከሩ፡፡ ፍራኦል ጨዋታውን ባሸናፊነት የምወጣበት ምት ነች ብሎ ሲመታ እዮኤል ይመልስበታል፡፡ እዮኤል አሁን የወንድሞቼን ሽንፈት የምበቀልበት ምት ነው ብሎ ጥርሱን ነክሶ ሲመታ፤ ፍራኦል እግሩን አንስቶ ይመልስበታል፡፡ ብዙ ተፎካከሩ፡፡
እዮኤል አሸነፈ፡፡ ረሀቡን ረሳ፡፡ ደስ አለው፡፡ ናትናኤል ገባ፡፡ ወንድማሞቹ እነ እዮኤልና ናትናኤል ለመሸናነፍ ትግል ገጠሙ፡፡ እዮኤል ጥሩ እየተጫወተ ሳለ መሀል ላይ ሰውነቱ ጨርቅ ሆነበት፡፡ ደከመ፡፡ ሆዱ ጮኸ..አቅለሸለሸው፡፡ ወደ ላይ ሊለው ሲል፣ ጨዋታውን ትቶ አንድ ጥግ ላይ ባለ ድንጋይ ላይ ሄዶ ተቀመጠ፡፡
እናቱ “ልጆች” እያለች ወደ ቤት ገባች፡፡ እዮኤል ተጠቅልሎ በተኛበት ሆኖ፤
“አቤት!” አለ፡፡ ሠላምታም ሳትሰጠው “እ…አንተ ነህ?” ብላ አለፈች፤ እንደ ዋዛ፡፡ …ጓዳ ገብታ መንጐዳጐድዋን ጀመረች፡፡
እዮኤል ከተኛበት ተነስቶ ወደ እናቱ ሄደ፡፡
“እማ….”
“እ?”
“ቆሎ እንኳን የለም?” አላት ድምፁን አለሳልሶና ሀዘን አልብሶ፡፡
“የለም!” አለችው፡፡
“አሁን ደግሞ የእራት ሰዓት ደርሶ የለ እንዴ? ምንአስቸኮለህ ቀስ ብለህ ትበላለህ”
ቁጣዋን ስለፈራ፤ “እሺ” አለ፡፡ “እሺ” ብሎ ወደ አልጋው ተመለሰ፡፡ እና ጥቅልል ብሎ ተኛ፡፡ እንቅልፍ ግን አልወሰደውም፡፡ እንቅልፍም አልተኛም፤ የሆዱ ጩኸትም አልተቋረጠም፡፡ ሆዱ ውስጥ የሆነ ኦርኬስትራ ያለ መሰለው፡፡  ዜማው ሙሾ ነው፡፡ ምቱ ግን ልክ አይደለም፡፡ የተዘበራረቀ ነው፡፡ አንዴ በሐይል ይጮኻል፡፡ አንዴ ለስለስ ብሎ ይደመጣል፡፡ ግራ የገባው ኤርኬስትራ!
በረከትንና ናትናኤልን ከዚህ በፊት ጠይቋቸው ያውቃል፡፡ ስለ ማን? ስለ እናቱ፡፡
“በረከት” አለ እዮኤል
“አቤት!” አለ በረከት
“ናቲ!” አለ እዮኤል
“አቤት!” አለ ናትናኤል
“እማዬ ግን ለምንድነው የማትወደኝ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ ሁለቱንም አፈራርቆ እያየ፡፡
“ኧረ ትወድሃለች” አለ በረከት
“አትወደኝም” አለ እዮኤል
“ለምን አትወድህም? ትወድሃለች እንጂ?”  አለ ናትናኤል፡፡
ሁለቱም ሊያፅናኑት እየሞከሩ ነበር፡፡ እንጂ እውነቱን ያውቁታል፡፡ ምክንያቱ ተሰወራቸው እንጂ ውጤቱ ለእነሱም ግልፅ ነው ወይም ነበር፡፡ እናታቸው ወንድማቸው እዮኤልን አትወደውም! አራት ነጥብ፡፡ ለምን እንደሆነ ግን አያውቁም፡፡
…ፀጋውና ፅጌ የሚዋደዱ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ በፍቅር “እፍ” ያሉ ጥንዶች፡፡
የፅጌ ፍቅር ግን ለየት ያለ ነበር፡፡ ባልዋን አብዝታ ትወደዋለች፡፡ ችግር እንዲገጥመው፤ እንቅፋት እንዲመታው አትፈልግም፡፡ አብራው ውላ፣ አብራው ብታድር ትወዳለች፡፡ ጠረኑን እየማገች ለዘላለም ብትኖር ደስ ይላታል፡፡ ከውጪ ሲመጣ ቤቱን አስውባ የሚወደውን ምግብ ሰርታ ትጠብቀዋለች፡፡ እየበላ የሚበላ አይመስላትም፡፡ አሁን አሁን የሚራብ ይመስላታል፡፡ እየተጫወተ የሚጫወት አይመስላትም፡፡ ዝም ካለ የሚቆዝም ይመስላታል፡፡ እየሳቀ የሚስቅ አይመስላትም፡፡ እሷ እንደምትፈልገው ወይም በምትፈልገው ደረጃ ሀሴት የሚያደርግ አይመስልም፡፡
ፍቅርዋ የእናት እንጂ የሚስት አይመስልም፡፡ ትሳሳለታለች፡፡ ልጆች ወልዳ እንኳን ከልጆችዋ የበለጠ እሱን ትንከባከበዋለች፡፡ እሱን ትወደዋለች፡፡ እሱን ታፈቅረዋለች፡፡
“ልጆችሽስ?” ስትባል፤ “ተዋቸው ባካችሁ… እነሱ ከፀጋው በኋላ የመጡ ናቸው፡፡ በብቸኝነቴ ዘመን የተንከባከበኝና ደስታን የሰጠኝ ፀጋው ነው፡፡ በዚያ በብቸኝነት ዘመናችን ያልዋለልኝ ውለታ፣ ያላደረገልኝ ነገር አልነበረም፡፡” ትላለች፡፡
“ለልጆቼ የምሆነው ለባሌ ከሆንኩ በኋላ ነው፡፡” ብላ ትናገራለች፡፡
በእርግጥ ልጆችዋን ትጠላቸዋለች ማለት አይደለም፡፡ ትወዳቸዋለች፡፡ ሌላው ቢቀር ፍሬዎችዋ መሆናቸውን አትክድም፡፡ የእሱ ልጆች በመሆናቸው ብቻ እነሱን (ልጆችዋን) ወዳም ባይሆን ተገዳ ትወዳቸዋለች፡፡ የፀጋው የዘር ፍሬ ናቸው፡፡ ለዚህ ምክንያት ስትል ብቻ ትወዳቸዋለች፡፡
ምንም ይሁን ምንም የፀጋው ማስታወሻዎች፤ የፀጋው ማስረጃዎች ናቸው፡፡ የማትወደው የመጨረሻ ልጅዋን እዩኤልን ነው፡፡ “ገፊ ነው!” ትለዋለች፡፡ እንደ አባትዋ ገዳይ ትቆጥረዋለች፡፡ነፍሰ  - ገዳይ ይመስላታል፡፡ ክላሽንኮቭ አላነገበም፡፡ ጩቤ አልያዘም፡፡ ጦር አልነቀነቀም፡፡ ግን ትጠላዋለች፡፡
“ይሄ እርኩስ ባልተወለደ ኑሮ ምን ነበር?” ትላለች፡፡
ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ፀጋውና ፅጌ በፍቅርና በሰላም “እኔ ልሙትልሽ”፣ “እኔ ልሙትልህ” እየተባባሉ ይኖሩ ነበር፡፡ በመሀል እዮኤል ተፀነሰ፡፡ የሰው ህይወት ሊያጨናግፍ፤ እሷን ባል አልባ ሊያደርግ ተፀነሰ፡፡ ፅንስ ሳለ እንደ ማንኛውም እናት ልታየው ትጓጓ ነበር፡፡ “ልጄ!” ብላ ሆድዋን ትዳብስ፣ ታሻሽ ነበር፡፡
ሶስተኛውን ልጅዋን እንደ ሁለቱ ልጆችዋ ሁሉ በፍቅር የማሳደግ ተስፋ ነበራት፡፡ ከፀጋው ጋር እየተቀባበሉ ሲስሙትና ሲያጫውቱት ይታያት ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ ለምን?! …
ፅጌ ምጥ ያዛት፡፡ ጎረቤቶች ተሰብስበው ሆስፒታል ወሰድዋት፡፡ ፀጋው ስራ ቦታው ነበር፡፡ ተደውሎ ተነገረው፡፡ ስራውን ጥሎ እየሮጠ መጣ፡፡ ለምታምጠው ሚስቱ ብርታት ሊሆናት፡፡ ልጁ ከእናቱ ማህፀን እንደወጣ ለማየት፡፡ እና ሊስመው፡፡ መጣ፡፡ ሆስፒታሉ ጋ ደረሰ፡፡
ሚስቱና ልጁ ጋ ለመድረስ ተቻኩሎ ሲከንፍ፤ እሱ ያላየው፣ የቆመውን ታክሲ ደርቦ የሚመጣ አንድ መኪና አገኘው፡፡ ፀጋው ተገጨ፡፡ ውሎ አላደረም፡፡ ከሰዓታት በኋላ ህይወቱ አለፈ፡፡ ፅጌ እንደ እብደት ነገር ቃጣት፡፡ ጮኸች፡፡ አለቀሰች፡፡ የምትወደው፣ የምታፈቅረው ባልዋ መንገድ ላይ ቀረባት፡፡ እንደወጣ ወደ ቤቱ ላይመለስ እስከ ዘላለሙ ተለያት፡፡ ፅጌ ጭንቀት እንደ አዞ አፉን ከፍቶ ዋጣት፡፡ ሀዘን በላይዋ ላይ ጎጆውን ሰራ፡፡
አራስ ልጅዋን ማጥባት እንኳን አስጠላት፡፡ እስከነመፈጠሩም ረስታ ከባልዋ ጋር ያሳለፉትን መልካም ጊዜ እያስታወሰች፤ በትዝታ ተሰቃየች፡፡
“እግዜር ያመጣው ነው” አሏት ጎረቤቶችዋ
“ቻይው፤ … እግዚአብሔር ልጆችሽን ያሳድግልሽ!”
“እግዜር ያመጣው አይደለም፡፡” አለች ፅጌ
“ይሄ የተረገመ ልጅ ያመጣው ነው፡፡” ወደ አራሱ ልጅዋ እያየች፡፡
ባልዋን በአጭሩ የቀጨባት እሱ እንደሆነ አሰበች፡፡
“ገፊ የሆነ ልጅ!” አለች፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ለእዩኤል ሆድዋ አልተፈታም፡፡ አቄመችበት፡፡ ልጅ መስሎ አልታይሽ አላት፡፡
“የባሌ ነፍሰ ገዳይ ነው” ብላ ደመደመች፡፡
ለምን?!
“እሱን ለመውለድ ሆስፒታል ባትገባ ኖሮ፤ ተደውሎ ባይነገረው ኖሮ፤ ልጁን ለማየት ባይጓጓ ኖሮ፤ ወደዚህ አይመጣም ነበር፡፡ ወደዚህ ባይመጣ ኖሮ ደግሞ አይገጭም ነበር፡፡ ባይገጭ ኖሮ  አይሞትም ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ጣጣ ያመጣብኝ ይህ ልጄ ነው፡፡”
እና ለልጅዋ እዩኤል ያላት ፍቅር እንደ ሁለቱ ልጆችዋ በረከትና ናትናኤል ሊሆን አልቻለም፡፡ የልጅዋ ዓይን ውስጥ እየያች ባልዋ ፀጋውን ታስታውሳለች፡፡ ስሙ ሲጠራ ፀጋውን ስታውሳለች፡፡ ስታየውም ፀጋውን ታስታውሰዋለች፡፡ እዩኤል ራስ ምታትና የጭን ቁስል ሆነባት፡፡ እንዳታባርረው ልጅ ሆነባት፡፡ እንደ ልጅ እንዳትንከባከበው ሆድዋ እምቢ አላት፤ ገፊነቱ ከዓይንሽ አልጠፋ አላት፡፡ “የባሌ ነፍሰ ገዳይ” የሚል ሀሳብ ተፈታተናት፡፡ እና እዩኤልን አትወደውም፡፡ …
… የእራት ሰዓት ደረሰ፡፡ ልጆችዋ ሁሉ ለእራት ተጠርተው ጠረጴዛው ዙሪያ ታደሙ፡፡ በረከትና ናትናኤል አልበላም ሲሉ በግድ ተለማምጣና ለምና ታበላቸዋለች፤ እዩኤል በላ አልበላ ግን ግድ የላትም፡፡ አሁን እራት ቀርቧል፡፡ አራቱም ሳህናቸውን አነሱ፡፡ ለበረከትና ናትናኤል እፍታ እፍታውን ጨመረችላቸው፡፡ አጥንት አጥንቱን ሳህኖቻቸው ላይ ከመረች፡፡ ለእዩኤልም ከወጡ ሰጠችው፡፡ አጥንት ግን አልደረሰውም፡፡ ተከለከለ፡፡ በረከትና ናትናኤልን ማጉረስ ጀመረች፡፡ ሁለቱን ካጎረሰች በኋላ እንጀራ ስትጠቀልል “እኔንም ልታጐርሰኝ ነው” ብሎ ጠበቀ እዩኤል፤ አላደረገችውም፡፡ ለራስዋ ጎረሰችውና በረከትንና ናትናኤልን ደጋግማ ወደማጉረሱ ገባች፡፡
የእዩኤል የልጅ ልብ ሀዘን ቋጠረች፡፡ እንባው መጣ፡፡ ምግቡን ትቶ ተነሳ፡፡ ፅጌ ምንም አላለችውም፡፡ ናትናኤል “ወዴት ነው?” ሲል ጠየቀው፡፡
“እዚሁ ነኝ መጣሁ!” ብሎ ሲወጣ በረከት “ምን ሆነህ ነው? ና ብላ እንጂ!” አለው፡፡
“እሺ!” ብሎት ወደ መኝታ ክፍሉ አመራ፡፡
በረከትና ናትናኤል ይወዱታል፡፡ ከእነሱ ጋር እንዲበላ እንዲጠጣ ይፈልጋሉ፡፡ የእናታቸው ድርጊትም አያስደስታቸውም፡፡ ልጅ ስለሆኑ አፍ አውጥተው ሊነግርዋት ፈርተው እንጂ ቢናገርዋት፣ ቢቆጥዋት ይወዳሉ፡፡ ግን አልሆነም፡፡
እናት ከፋች! ታዲያ እነሱ ምን ያድርጉ?! እዩኤል አልጋው ላይ ወጥቶ ተጠቅልሎ ተኛ፡፡  

Published in ልብ-ወለድ