አየርላንዳዊው ደራሲ ጀምስ ጆይስ፤ “ዩሊሰስ” (Ulysses)፣ “ደብሊነርስ” (Dubliners) እና “A Portrait of the Artist as a Young Man” በተሰኙ ስራዎቹ ይታወቃል፡፡ ይሄ ደራሲ በአንድ ወቅት “A Brilliant Career” የተሰኘ ድራማ ፅፎ ለአሳታሚው ይሰጠዋል። አሳታሚው ሳይወድለት ይቀራል፡፡ ዳግም ሲያነበው እውነትም ሊወደድ እንደማይችል ይረዳል፡፡ በመሆኑም ረቂቁን የሚንቀለቀል እሳት ውስጥ ጨምሮ አቃጠለው፡፡
ይሄን ታሪክ ያነበብኩ እለት አንዳች አመፅ በሰውነቴ ውስጥ ተሰራጨ፡፡ ደራሲው ለድርሰቱ ምንድነው? ጌታ? ባለቤት? ወይስ አምላክ? ሸክላ ሰሪ በገንቦው ላይ ካለው መብት አይለይም? ካልፈለገው መስበር፣ ማንኮታኮት፣ ማድቀቅ … ይችላል? የደራሲው ውሳኔና ምዘና የሚያስከትለው ጉዳት ከደራሲው አልፎ የሚሸጋገር አይደለምን? ሀዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር”ን ሳያሳትሙ ቢያቃጥሉትስ ኖሮ? ጉዳቱ የእሳቸው ብቻ ነበር? እሳቸውን ተከሳሽ፣ እኛን ሞጋች አያኳኩነንም ነበር? ለመሆኑ ጉዳታችን በምን ይመዘናል? …
… እኛም ሀገር እንዲሁ እንደ ጆይስ ያደረገ ደራሲ ነበር። ባሴ ሀብቴ ነው፡፡ “ወንድም ጌታ” የተሰኘ ቤሳ ልቦለዱን ጨርሶ ጥቂት ሰዎች ካነበቡት በኋላ አቃጠለው። እንደ ጆይስ ሳይወደድለት ቀርቶ አይደለም፡፡ እንደውም፣ ተወድዶለት ነበር፡፡ ይሁንና “ወንድምጌታ” እንደ “A Brilliant Career” ተቃጥሎ ከመቅረት የሚታደገው አገኘ፡፡ ስንዱ አበበ  ዳግም እንዲፃፍ አደረገችና ስራውን ከደመኛው ፈጣሪው ነጥላ አኖረች፡፡ ባሴ ከሞተ በኋላ እንዲታተም አደረገች፡፡ ትልቅ ውለታ!!
የድመት ነፍስ ያላቸው አንዳንድ ደራሲዎች አሉ፡፡ ፈቃዳቸውን የተጠለለ “ግልገል” ሥራቸውን ለመብላት የማይመለሱ፡፡ ከተፈጥሮ ውጭ የከሳሽነት መብት የሌለባቸው መሆኑ ሳያበረታታቸው ይቀራል? የቼኮዝላቫከሊያ ተወላጅ የሆነው ደራሲ ፍራንዝ ካፍካ (Franz Kafka) ማክስ ብሮድ (Max Brod) ለተሰኘ ጓደኛውና ለህይወት ታሪኩ ፀሐፊ የተናዘዘው አብዛኛዎቹ ስራዎቹ እንዲቃጠሉለት ነበር፡፡ የካፍካ መዳከም ጉልበቱን በኑዛዜ ገደበበት እንጂ ተነስቶ የማሰባሰብና የመለኮስ አቅም ቢኖረውስ ኖሮ? ብሮድ የጓደኛዬን ኑዛዜ ልሙላለት ቢልስ ኖሮ? … የአንድ ሰሞን ታሪካዊ ገፅታችን የነበረው ወፈፍታ (Age of Anxiety) በካፍካ ስራዎች ውስጥ ህያው ሆነው መቅረባቸው ይቀርብን ነበር፡፡ ጉዳቱ በምን ይመዘን ነበር? …
… የማያውቁት መፅሐፍ አይናፍቅም ካላልን በስተቀር ከየትኛውም ጉዳይ በላይ የጥበብ ስራዎች መብከንከን ህብረተሰብ ጎጂ ነው፡፡ ዕንቁ፣ አልማዝ፣ ወርቅ፣ ጨርቅ፣ መሬት ተከፍቶ ቢውጠው የተመለሰው ወደመጣበት ነው፡፡ ሀብት ንብረት ቢወድም የትም አልሄደም፡፡ የጥበብ ስራ ግን አይተኬ ጉዳት ነው፡፡ ይሄንን በጥንቶቹ የግሪክ ፀሐፌ ተውኔቶች አረጋግጠናል። ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ525-456 የኖረው ኤስኪለስ (Aeschylus) የጭፍግግ ቴአትሮች አባት (father of tragedy) በመባል ይታወቃል። የዘመኑን ገፅታ ጠንቅቀን የተረዳነው ኤስኪለስ የግሪክ ታሪክ፣ አፈታሪክ እና ህይወት ላይ ተመስርቶ በፃፋቸው ተውኔቶች ነው፡፡ በዚህ ፀሐፌ ተውኔት ላይ የተሰሩም ምርምሮች እንደሚስረዱት፤ ከሰባ እስከ ዘጠና የሚሆኑ ቴአትሮችን ፅፏል ይሁንና በዚህ ጊዜ ተርፈው የተገኙት ሰባቱ ብቻ ናቸው፡፡ እንደ ግንባታ ፍርስራሻቸው፣ እንደ ሀውልት ጉማጃቸው ያልተገኘ ከስልሳ ሶስት እስከ ሰማኒያ የሚደርሱ ብርቆች የት ገቡ? …
የሌላኛው ግሪካዊ ፀሐፌ ተውኔት የሶፎክለስም ስራዎች እንዲሁ የአስማት ድግምት መስለው ጠፍተዋል፡፡ ሶፎክለስ (ከክ.ል.በፊት 496-406) በአጠቃላይ የፃፋቸው ተውኔቶች 123 እንደነበሩ ተመዝግበው ተገኝተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እኛ በንብረትነት የምንቆጥራቸው ግን ሰባት ብቻ ናቸው፡፡ አይቆጭም? አያንገበግብም?
የጊዜ ጥሻ ጉድባው ብዙ ነውና በዚህ ረጅም ዘመን ውስጥ ያዝረከረክነው የጥበብ ውጤት ህልቆ መሳፍርት ያለው አይመስልም፡፡ አሁን በቅርብ ዘመን እንኳን (1922 ዓ.ም) አሜሪካዊው ደራሲ ኤርነስት ሐሚንግዌይ የፃፋቸው ሃያ አጫጭር ልቦለዶችና አንድ ለመጠናቀቅ ጥቂት የቀረው አንደኛው ዓለም ጦርነት ላይ የሚያተኩር ልቦለድ ጠፍቶበት ቀርቷል፡፡ አጠፋፉ እንዲህ ነው፡፡ የሔሚንግዌይ ባለቤት ኤልሳቤት ሪፖርድሰን ያልታተሙ ስራዎቹን ሁሉ ሸክፋ ስትጓዝ ከመካከል እነዚህን ስራዎች የያዘው ሻንጣ ይሰረቃል፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እርዳታ ለማፈላለግ ቢሞከርም ስራዎቹ ሳይገኙ ይቀራሉ። መቼም ሌባው የስራዎቹን ጥቅም አውቆ አልሰረቀም፤ ገንዘብና ልብስ ጠብቆ “የወረቀት” ክምችት ሲያጋጥመው ምን አድርጎት ይሆን? በእልህ ቦጫጨቀው? ወይስ እንደኛ ሌቦች ለሱቅ በኪሎ ሸጠው? … እኛ ከሰርን እንጂ መቼም ሌባው እንዳልተጠቀመ እሙን ነው፡፡
ወደኛ እንምጣ …
… አንድ ጊዜ ከደራሲ አስፋው ዳምጤ ጋር ስንጨዋወት አንድ አስገራሚ ጥቆማ ሰጡኝ፡፡ ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር አሁን ካሉት ልቦለዶቹ በተጨማሪ አንድ ማንበባቸውን፡፡
“ሌቱም አይነጋልኝ ይሆን?” አልኳቸው፡፡
“አይደለም - ከእሱ ያንሳል፡፡ ሌቱም አይነጋልኝን ያኔ አንብቤው ነበር፡፡ በእስክሪፕቶ የተፃፈውን፡፡ የጠፃፈበት መዝገብ ሲያልቅ ወረቀቱ ጀርባ ላይ ወደኋላ እየተፃፈበት ነው ታሪኩ የሚጠናቀቀው፡፡ ይሄ የምልህ እሱ አይደለም”
“ሰባተኛው መልአክ ይሆን?”
“ከእሱ ከፍ ይላል፡፡ አራተኛ ትልቁ ስራው ይመስለኛል፡፡”
የት? እንዴት? … ተብሎ ይፈለጋል? ልቦለዱስ ስለምን ያትታል? የትኛው ግሩም ገለፃ ቀረብን? ምን አዲስ ነገር አጣን? የትኛዋ ገፀ ባህርይ እንደ በረዶ ሟሙታ ጠፋች? … በድቅድቅ ጨለማ ላይ ማፍጥ ሆነብኝ፡፡ ዱካ የማይተው ጥፋት!!
መፅሐፍ ሲጎድል ባይታወቅም የመጉደል ውጤቱ ግን ዘልአለም ከእኛ ጋር ይኖራል፡፡ ሥነ-ፅሁፋችን አዝጋሚና ቀር ለመሆኑ ምክንያት አንዱ የስራዎች መብከንከን ሳይሆን ይቀራል? ምን ያህል ሸካፊዎ ሆነን ማንጠባጠብ እንደጀመን አይገባኝም፡፡ እንደ ቤት ለቃቂ ወንደላጤ የሥነ ፅሁፍ ጓዛችን ቢሸከፍ ከአንድ ከረጢት ያልፋል? አንድ ሲጎድል፣ እንዴት አይቀለንም? …
ቀኝ አዝማች ተወንድበላይ ባቢቼቭ የሚባሉ አንድ ሰው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፣ በንጉሱ ትዕዛዝ የዳንቴ አሊጌሪ ሶስት ስራዎች ወደ አማርኛ መልሰዋል፡፡ አንዱ Hell “ሲኦል” በሚል ርዕስ ታትሟል፡፡ ሁለቱ “Heaven” እና “Pulgatory” ግን ቢተረጎሙም ሳይታተሙ ቀርተዋል፡፡ ቀኝ አዝማች በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ስራዎቹ የት እንዳሉ እንኳን ማረጋገጥ የሚቻል አልሆነም፡፡ እነዚህ ሁለት ስራዎች የት? እንዴት? … ባለ ሁኔታ ይገኙ ይሆን? ጥቅማቸውን የማይረዳ ሰው እጅ ገብተው ተጎሳቁለው፣ ወይም እሳት ማያያዣ ሆነው ይሆን? ማንም የሚያውቅ የለም፡፡
እስኪ ደግሞ ወደ አሮጌ መፅሐፍቶች ጥቆማ እንሂድ፡፡ የተለያዩ ብዙ መፅሐፍት ወደፊት በደራሲው ተዘጋጅተው ለመታተም የደረሱ ስራዎች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ እጃችን ሳይደርሱ ቀልጠው የቀሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” የተሰኘው የዶ/ር እጓለ ገብረዮሐንስ መፅሐፉ፣ የጀርባ ገፆቹ ላይ ሶስት አጓጊ የፍልስፍና ስራዎች ያስተዋውቀናል። “ሥነ-ምግባር”፣ “ከተረት ወደ ሕሊና” እና “ፋውስት” የተሰኙ፡፡ በስራዎቹ ላይ አጫጭር መግለጫም ተሰጥቷል፡፡ ስራዎቹ ከተዋወቁ ግማሽ ምዕተ ዓመት ቢያስቆጥሩም እስከዛሬ ፍንጫቸው አልታየም። እንደ ሐሌ-ኮሜት ሰባ ዓመት ሲሞላቸው ይመጡ እንደሆን ከመጠበቅ ውጭ ሌላ ምን አማራጭ አለን?
በእንጥልጥል ከቀረ ሃምሳ አምስት ዓመታት ያስቆጠረ ሌላ ቃልኪዳን አለ፡፡ ተመራማሪው መስፍን ልሳኑ ሲባሉ የሥራቸው የመጀመሪያ ክፍል “የአማርኛ መጽሔት ቃላት” በሚል ርዕስ ያኔ ታትሟል፡፡ ሥራው የሚያተኩረው ባለአንድና ባለሁለት ፊደላት የአማርኛ በአማርኛ ፍቺ ላይ ነው፡፡ ያልታተሙት ቀጣዮቹ ሥራዎቹ በፊደላቶቹ ቁጥሮች መጠን በቅደም ተከተል ተሰርተው እንደተጠናቀቁ ተመራማሪው ገልፀዋል፡፡ መፅሐፉ መቼም ግሩም ነበር፡፡ አንዲት ፊደል ከተርታ ሰልፏ አንስቶ እስከ ፍቺዋ ድረስ ተሟልታ ተተርጉማ ትታያለች - “ኣ”ን እንዴት እንዳገላበጧት እንይ፡-    
ኣ = የአ፡ ራብዕ፡፡ ፪ ውጋት የያዘው ሰው ሲያቃስት የሚያሰማው ድምፅ፡፡ ኣ! ኣ! እንዳለ አደረ፡፡
የዚህ መፅሐፍ ቀጣዮቹ ስራዎች አልታተሙም፡፡ መፅሔተ ቃላቱ በአንድና ሁለት የፊደል ቁጥር ባላቸው ቃላት ላይ ተንጠልጥሎ ቀርቷል፡፡ ማን እጅ፣ በእንዴት ያለ ሁኔታ ውስጥ ይሆን? …
… በዚህ መንገድ ከቀጠልን መዳረሻ አልባ ጉዞ ይሆንብናል፡፡ በይበልጥ ቆየት ያሉ የአማርናኛ ሥነ-ፅሁፍ ስራዎችን ስንፈትሽ፣ አብዛኞቹ መጪ ስራዎቻቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ግን ሳይታተሙ የቀሩት ያንኑ ያህል ብዙዎች ናቸው፡፡ ይሄን በዚህ ገትተን ወደሌላኛው ገፅታ ደግሞ እንተላለፍ፡፡ ከስነ-ፅሁፍ መሸከፊያ ከረጢታችን ጎድሎ ከቀረው፣ ለመጉደል የተዘጋጀው ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ በዚህ ዘመን የህትመት ቀልባችንን ገበያ መራሽ ስራዎች ላይ በመጣላችን ጠነን ያሉ ወጥ ስራዎና ትርጉሞቸ የተስፋ መቁረጥ አፈር እየተመለሰባቸው ይገኛል፡፡
ከሶስት ወይም ከአራት ዓመታት አስቀድሞ የግሪካዊው ደራሲ የኒኮዝ ካዛንትዛኪዝ (Nikos Kazantzakis) ልቦለድ “ዞርባ ዘ ግሪክ” (Zorba the Greek) እንደተተረጎም አውቃለሁ፡፡ ተርጓሚው ተፈሪ መኮንን ነው፡፡ እስካሁን አልታተመም፡፡ የዚህ ስራ አለመታተም በሥነፅሁፍ ምርጫ ላይ የት እንዳለን የሚጠቁም ይመስላል፡፡ ምናልባትም ገለብ ገለብ ያሉ ስራዎች ሳይበርዱ ከተርጓሚ ወደ አሳታሚ እጅ የመተላለፋቸው ፍጥነት ስራ አብዝቶ ይሆናል፡፡ እነዚህኞቹ ተመልካቾች ያጡት የካዛንትዛኪዝ ስራዎች በተለይም “ዞርባ ዘ ግሪክ” ለአማርኛ ሥነ-ፅሁፍ ያለው ጠቀሜታ ከዚህ መለስ የሚባል አይደለም፡፡ በተለይ የስብሐት ገብረእግዚአብሄር ስራዎች እስከዛሬ ከታዩበት አግባብ ውጭ እንዲገመገሙ የሚያስገድድ ልቦለድ ይመስለኛል፡፡
በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት መጠናቀቂያ ላይ አንጋፋው ደራሲ እና ተርጓሚ ሳህለ ሥላሴ ብርሃነ ማሪያም አንድ ትልቅ ስራ ተርጉመው እንደጨረሱ ከራሳቸው አረጋግጬ ነበር፡፡ ስራው የፈረንሳይ ፀሐፊ የኦርነስት ረና “ቬ.ደ ዠዚ” (Vie D. Jesus) ነው፡፡ የእንግሊዝኛ ትርጉሙ “Life of Jesus” ሲሆን ሳህለ ሥላሴ “የየሱስ ህይወት” ብለው ወደ አማርኛ መልሰውታል፡፡ ይሄን መጣጥፍ ለመፃፍ ሳስብ ወደ ተርጓሚው ዘንድ ስልክ መትቼ ነበር፡፡ አሳታሚ አግኝቼ የለቀማ ስራ በማከናወን ላይ ነኝ ብለውኛል፡፡ ልብ ልንገዛ ይሆን?
ሌላው አንጋፋ ደራሲ አስፋው ዳምጤ የጄን አውስተንን ሥራ ከአገሩ ከእንግሊዝ፣ ወዲህ በኛ ቋንቋ ጠልፈው ጨርሰው እንደነበረ ነግረውኛል፡፡ ጋሽ አስፋው የተረጎሙት “Pride and Prejudice”ን ነው። ለአውስተን ሽሙጥ እና አሻሚ የአፃፃፍ ስልት ልከኛው ተርጓሚ ጋሽ አስፋው እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡
የመፅሐፍ ሾተላይ ምንጩ ከደራሲው ይጀምራል፡፡ ደራሲ እንደ ድመት ግልገሉን ከመብላቱ በፊት እራሱን መገሰጫ ምክንያት ሊያበጅ ይገባል፡፡ በእንዴት ያለ አእምሯዊ ነባራዊ ሁኔታ ተጻፈ? ከማጥፋት ማሻሻል አይቀድምም? ባንወደውስ፣ ቢቀመጥስ ምን ይጎዳናል? ስንት ስራዎች በዘመናቸው ተቀባይነት ሳይኖራቸው ቀርቶ በኋላ ተወዳጅ ሆኑ? የምናቃጥለውስ ከዘመኑ ጋር አልገጥም ብሎ ቢሆን? …
ቀጣዩ የመፅሐፉ ሾተላይ የደራሲው ወራሾች ላይ ያርፋል፡፡ የሥነ-ፅሁፍ ስራዎች ብዙ ጊዜ ከደራሲው ቤተሰቦች ጋር ደም የተቃቡ ይሆናሉ፡፡ ጊዜ፣ ፍቅር፣ ትኩረት … ይሻማሉና፡፡ ስለዚህ ደራሲው ስራዎቹን ከቤተሰቦቹ ጋር የማስታረቅና የማዋደድ ስራ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም ደራሲው “ዞር ሲል” ከመቃጠልና ከመጥፋት ይድናሉ። መፅሐፎቹ በረቂቅ ሳይሆን በህትመት የተሰራጩም ቢሆኑ በወራሾች ቂም ከተያዘባቸው ለዳግም ህትመት እንዳይበቁ እንቅፋት ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አንድ ገጠመኜን ጣል አድርጌ ላብቃ፡፡
አንድ አንጋፋ ደራሲ ከዚህ ኣለም በሞት ከተለየ በኋላ ስራዎቹ ከገበያ በመጥፋታቸው ከአሳታሚዎች ጋር ሆኜ ወራሾቹን ማፈላለግ ይዤ ነበር፡፡ ስለዚህ ነገር ያነሳሁባቸው አንድ አንጋፋ ደራሲ “ነገሩ ወዲህ ነው” አሉኝ፡፡
“ምን?” አልኳቸው
“ልጆቹ እንዲታተም የሚፈልጉ አይመስለኝም”
“ለምን?”
“ደራሲው እኮ በልጅነታቸው እርግፍ አድርጎ ጥሏቸው ከቤት የወጣው ስራዎቹን ለማጠናቀቅ ነው፡፡”
“ስለዚህ?”
“ስለዚህማ ስራዎቹ ለልጆቹ ደመኞች ናቸው፡፡ ቢጠፉ የሚመርጡ ይመስለኛል፡፡”
እንዲህም አለ፡፡  

Published in ጥበብ

በጋዜጠኝነት ከ15 ዓመታት በላይ ሰርቻለሁ፡፡ አድማስን ገና ሲጀመር አንስቶ ነው የማነበው፡፡ ጋዜጣውን እንደ ጋዜጣ ብቻ አልነበረም የምመለከተው፡፡ ከጋዜጣም በላይ ስነ-ፅሁፋዊ የረቀቀ ባህሪ ነበረው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በጋዜጣው ላይ ይፅፉ የነበሩት ከዋና አዘጋጁ ጀምሮ እነ አብረሃም ረታ፣ ጋሽ ስብሃት… የረቀቁ የስነ-ፅሁፍ  ሰዎች ስለነበሩና መስራቹ አሰፋ ጎሳዬም የዚሁ ዓይነት ባህሪ ስለነበረው ይመስለኛል፡፡
ጋዜጣውን ዝም ብለሽ ስትመለከቺ፣ ሌላው ቀርቶ ርዕሰ አንቀፁ እንኳን በቅርፅና በይዘቱ የተለየ ነው፡፡ አዲስ አድማስን እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ እስከተወሰነ ጊዜ ያለማቋረጥ እንገዛና ጠርዘን እናስቀምጥ ነበር፡፡ ዜናው አካባቢ ሳሳ ያለ ባህሪ ስለነበረው ዜናውን አየት አየት አድርጌ ሌላ ጊዜ እየተመላለስኩ ፅሁፎቹን፣ ትንታኔዎቹን በማንበብ እመሰጣለሁ፡፡ በዚያ ላይ እኔም አዲስ አድማስ ላይ እፅፍ ነበር፡፡ ጋዜጣውን የተለየ የሚያደርገው በግራም በቀኝም ፅንፍ አለመያዙ ነው፡፡ መሃል ላይ ሆኖ በሰከነ አካሄድ 15 ዓመታትን መጓዝ ቀላል አይደለም፡፡ ከአጀማመሩ አንፃር አሁን የሚገኝበት ደረጃ ትንሽ ክፍተት ይታይበታል፡፡ ለዚህ ነው ሥራ የጀመረው ከከፍተኛ ደረጃ ነው ማለቴ፡፡ ከሌይአውት፣ ከፅሁፍ ይዘትና ከገፅ ብዛት አንፃር መሻሻል ያለበት ነገር ቢኖርም 15ኛ ዓመቱ ላይ መድረሱ ያስደስተኛል፡፡ ከዚህ በተሻለ ይዘት ሌሎች 15 ዓመታትን እንደሚጓዝ ምኞቴ ነው፡፡

Published in ጥበብ

የመፅሀፍት ገበያውን ማን ይመራዋል?

    ይትባረክ አለሜ ከሰሜን ሸዋ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ ከስድስት ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል በጥበቃና በሆቴል ተላላኪነት ከሰራ በኋላ በጓደኛው ግፊት መፅሀፍ አዟሪ ሆነ፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታትም በአራት ኪሎና አካባቢዋ እየተዘዋወረ መፃሕፍት ሲሸጥ ቆይቷል፡፡ መፅሀፍ አዟሪነት ብዙ አትራፊ ባያደርግም ጦም አያሳድርም የሚለው ይትባረክ፤ እንደ “ዴርቶጋዳ” ያሉ መፃሕፍት ገቢውን እንዳሳደጉለትና ከእለት ጉርሱ አልፎ ገንዘብ ማስቀመጥ እንጀመረ ይናገራል፡፡
“የአዲስ አበባ ጉዶች”ና “የተቆለፈበት ቁልፍ” ታትመው ሲወጡ በኑሮአቸው ላይ ልዩነት መፍጠራቸውን የሚገልፀው  አዟሪው፤ በቅርቡ “ታወር ኢን ዘ ስካይ” የተባለው የህይወት ተፈራ መፅሀፍ “ማማ በሰማይ” በሚል ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በደንብ ሲሸጥ እንደነበር ጠቁሞ ሰሞኑን ግን የ“ዴርቶጋዳ” ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ያወጣው “ዩሮቶራድ” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ ገበያውን እንደተቆጣጠረው ገልጿል፡፡
ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በመፅሐፍ አዟሪነት የሰራው ፍሰሃ የተባለ ወጣት እንደሚናገረው፤ እስካሁን “የዴርቶጋዳ”ን ያህል የተሸጠ መፅሀፍ የለም፡፡ “ዴርቶጋዳ ምን ታምር እንዳለው አላውቅም፤ ብር ያስቆጠረን እሱ ነው ያለው” አዟሪው፤ መፅሀፍ የማንበብ ልምድ ባይኖረኝም “ዴርቶጋዳ”ን አንብቤ ተገርሜያለሁ ብሏል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት ከይስማዕከ መፃሕፍት ጋር ባይወዳደሩም ለአዟሪዎች ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የሆኑ መፃሕፍትም ወጥተዋል፡፡ “የአዲስ አበባ ጉዶች”፣ “ዣንቶዣራ”፣ “ክቡር ድንጋይ”፣ “ራማቶሃራ”፣ የተቆለፈበት ቁልፍ” እና፣ የመሳሰሉት መፃህፍት በተደጋጋሚ እየታተሙ እንደተሸጡ አዟሪው ተናግሯል፡፡ ሰሞኑን እየተሸጠ ያለው የይስማዕከ አዲሱ መፅሃፍ ቢሆንም “ማማ በሰማይ” ብዙ ፈላጊ እንዳለው  ፍስሃ ገልጿል፡፡
ስድስት ኪሎ አካባቢ ያገኘሁት የ38 ዓመቱ መፅሀፍ አዟሪ ብዙአየሁ ለ14 ዓመታት ከመፅሀፍ ሽያጭ ሥራ አልተለየም፡፡ አንጀቱ ላይ ጠብ ያለው ግን እነ “ዴርቶጋዳ” እና ተከታዮቹ “ራማቶሃራ”፣ “ተከርቸም”፣ “ክቡር ድንጋይ”፣ “ተልሚድ”ና “ዣንቶዣራ” የመሳሰሉ መፃህፍት ከታተሙ በኋላ እንደሆነ ይናገራል፡፡ “እርግጥ ከዚያ በፊት የኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም ማስታወሻ እንዲሁም በ1994 ዓ.ም የታተመው የደራሲ ዘነበ ወላ “ልጅነት”ን አብዝቼ በመሸጥ መጠቀሜን አስታውሳለሁ” ይላል መፅሐፍ አዟሪው፡፡ የመፅሀፍ አብዮት የመጣው ግን ከ“ዴርቶጋዳ” መታተም በኋላ ነው ባይ ነው፡፡ “ፒያሳ ማህሙድ ጋር ጠብቂኝ”፣ “የአዲስ አበባ ጉዶች”፣ “የፍቅር ኬሚስትሪ”፣ “የተቆለፈበት ቁልፍ” እና “ማማ በሰማይ” የተሰኙት መፃህፍት ብዙ መሸጣቸውን የገለፀው ብዙአየሁ፤ ሰሞኑን ገበያውን የተቆጣጠረው ግን “ዮሮቶራድ” እንደሆነ ተናግሯል፡፡
አንዳንድ አዟሪዎች የመፅሐፍ ገበያው በዚህ ከቀጠለ የመፃህፍት መደብር የመክፈትና አሳታሚ የመሆን ዕቅድ እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ ሌሎቹ አዟሪዎች ከጠቀሷቸው መፃህፍት በተጨማሪ “የአበሻ ጀብዱ” የተባለው መፅሃፍ ብዙ እንደተሸጠ የጠቆመው የመርካቶው አዟሪ ኡስማን መሃመድ፤ ሥራው አትራፊ እየሆነ በመምጣቱ ታናሽ ወንድሙም ፒያሳ  አካባቢ መፅሃፍ ማዞር መጀመሩን ተናግሯል፡፡
ከመፃህፍት ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ ደስተኛ መሆኑን ጠቁሞ፤ “ደራሲዎቻችንን ፈጠራ ያፍስስባቸው” ሲል መርቋቸዋል፤ መፅሃፉ አዟሪው፡፡
በቅርቡ ወደ መፅሐፍ አሳታሚነትና አከፋፋይነት የገባው የባህሩ መፅሐፍት መደብር ባለቤት አቶ ባህሩ ሰለሞን፣ ብዙ መፃሕፍት የሚሸጡት በይዘታቸው ሳይሆን በቲፎዞ መሆኑን ይናገራል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት ከወጡት መፃህፍት መካከል “የኮሎኔል መንግስቱ ማስታወሻ”፣ የዘነበ ወላ “ልጅነት”፣ በቅርቡ ደግሞ የዶ/ር ምህረት “የተቆለፈበት ቁልፍ” ለእኔ ምርጥ መፅሀፍት ናቸው ብሏል - አሳታሚው፡፡ በዘንድሮው የገና ባዛር ላይ በኤግዚቢሽን ማዕከል ብቸኛውን የመፅሀፍ፣ ስታንድ ገዝቶ መፃሕፍትን የሸጠ ሲሆን “የተቆለፈበት ቁልፍ” በብዛት እንደተሸጠለት ገልጿል።
“መፅሀፉ ትልቅ ማህበራዊ ጉዳዮችን ስለሚያነሳና  ጠንካራ ገፀ ባህሪያት የተሳሉበት በመሆኑ ያለ ቲፎዞ የሚሸጥ ነው” ብሏል፡፡
“ማማ በሰማይ” በሚል የተተረጐመው የህይወት ተፈራ መጽሐፍ በጣም እየተሸጠ እንደሆነ የገለፀው አሳታሚው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በታተመበት ወቅት ገዢ ያላገኘው የዳኛቸው ወርቁ  “አደፍርስም”፤ አሁን በድጋሚ ታትሞ እየተሸጠ ነው ብሏል፡፡
በዶ/ር ምህረት ደበበ ተፅፎ ራሳቸው ያሳተሙት “የተቆለፈበት ቁልፍ” በቃልኪዳን መፅሀፍት መደብር እየተከፋፈለ ሲሆን መፅሐፉ ለ7ኛ ጊዜ ታትሞ በጠቅላላ 35ሺህ ኮፒ መሸጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
“እስከ ዛሬ በሚታተሙት መፅሐፍት አሳታሚውም ደራሲውም አከፋፋዩም ብዙ አልተጠቀሙም” ያለው የቃልኪዳን መፅሃፍት መደብር ባለቤት አቶ ቃልኪዳን አምባቸው፤ “የተቆለፈበት ቁልፍ ደራሲ ግን ጠንካራ ይዘት ያለው መፅሀፍ በማምጣትና በጠንካራ ዋጋ በመሸጥ ሁሉንም ወገን እየጠቀሙ ነው” ብሏል፡፡
ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ አንድ የመፃህፍት መደብር ባለቤት፤ በበኩላቸው፤ ማን በሽያጭ መራ፣ የትኛው ይበልጥ ተነበበ… የሚለውን ጥያቄ በትክክል ለመመለስ ጥናት ማድረግ የግድ ነው ይላሉ፡፡ ለምን ቢሉ? ታትመው ለገበያ የሚቀርቡ መፃህፍት ዓይነታቸው ብዙ ነው፤ በየዘርፉ ጥናት ተሰርቶ መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡
በመፅሐፍት ሽያጭ ገበያውን እየመሩት ነው ከሚባሉት ውስጥ የመሃመድ ሳልማን “ፒያሳ ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ” ተጠቃሽ ሲሆን መፅሀፉ እስካሁን 21ኛ እትም ላይ መድረሱንና 103ሺህ ኮፒ መሸጡን አከፋፋዩ ሊትማን መጽሐፍት መደብር ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ የአቤል አለማየሁ “የአዲስ አበባ ጉዶች” ለ8ኛ ጊዜ ታትሞ 40 ሺህ ኮፒ፣ የብርሃኔ ንጉሴ “የፍቅር ኬሚስትሪ”  ለ5ኛ ጊዜ ታትሞ 30ሺህ ኮፒ መሸጡንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ትክክለኛ ቁጥራቸውን ለማወቅ ባይቻልም “ሮዛ”፣ “ልጅነት”፣ “መረቅ”፣ “ማማ በሰማይ” ከፍተኛ ሽያጭ ካስመዘገቡት ውስጥ የሚመደቡ ናቸው ተብሏል፡፡
ከተለያዩ ምንጮች ባሰባስበነው መረጃ መሰረት፤ የመጽሐፍት ገበያውን በቀዳሚነት የሚመሩት የይስማዕከ ወርቁ መፅሀፍት ሲሆኑ “ዴርቶጋዳ” 25ኛ እትም ላይ ደርሶ እስካሁን 210 ሺህ ኮፒ ሲሸጥ፣ 15ኛ እትም ላይ የደረሰው “ራማቶሃራ” 115ሺህ፣ ዣንቶዣራ በ8ኛ እትም 105ሺህ፣ “ተከርቸም” አምስተኛ እትም 65ሺ፣ “ክቡር ድንጋይ” በ6ኛ እትም 95ሺህ፣ “ተልሚድ” በ4ኛ እትም 85ሺ፣ “የቀንድ አውጣ ኑሮ” እና “የወንድ ምጥ” የተሰኙት የግጥም መፃሕፍቱ (ሁለቱም) 55 ሺ እንዲሁም ሰሞኑን ያወጣው አዲስ መጽሐፉ “ዩሮቶራድ” 45ሺ ኮፒ ተሸጦ ሁለተኛ ዕትም ላይ እንደሆነ ታውቋል። የመጀመሪያ ሥራው “ዴርቶጋዳ” ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱ ተከታዮቹ ሥራዎች ላይ እንዲተጋ እንዳነቃቃው የገለፀው ይስማዕከ ወርቁ፤ የራሱን ማተሚያ ቤት ከፍቶ መፃህፍቱ እያሳተመ ተናግሯል፡፡
የደራሲው ሥራዎች ወደተለያዩ የውጭ ቋንቋዎች እየተተረጐሙ ሲሆን፡፡ “ዴርቶጋዳ” ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ እየተሸጠ መሆኑን ያስታወሰው ደራሲው፤ “ክቡር ድንጋይ” የተሰኘ መፅሀፉም ወደ ሩስኪ ቋንቋ እንደተተረጐመለት ተናግሯል፡፡ “ዴርቶጋዳ”ን ወደ ስፓኒሽኛ ለመተርጎም ፈቃድ መጠየቁን ጠቅሶ እሱ ግን ወደ ትግርኛና ኦሮምኛ እንዲተረጎምለት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል፡፡

Published in ጥበብ

(የአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት እንግዳ)

በአትሌቲክስ ዘርፍ በርካታ የዓለም ሪከርዶችን የሰበረው ታላቁ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ  ለ30 ዓመታት ባሳለፈው የሩጫ ዘመኑ (በተለይ በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች) ባገኘው የሽልማት ገንዘብ መጠን የዓለም አትሌቶችን በአንደኝነት ይመራል - ከ3.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመሰብሰብ፡፡ አትሌቱ ከሩጫው ጐን ለጐን ሲያካሂድ በቆየው የቢዝነስ ሥራውም ከፍተኛ ስኬትን ተቀዳጅቷል፡፡ ከተሰማራባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል ሲኒማ፤ ሪልስእቴትና ኮንስትራክሽን፤ ሆቴልና ሪዞርት፤ ማእድን፤ ቡና እና አትሌቲክስ ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ የቢዝነስ ዘርፎችም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እያንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ፤ ከአትሌቱ ጋር ባደረገው ሰፊ ቃለምልልስ የቢዝነስ እንቅስቃሴውን፣ የአሰራር መርሁን፣ የኢንቨስትመንት ራዕይና ዕቅዱን እነዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን ፈትሿል፡፡ በአትሌቱ ቢዝነስ ላይ ያተኮረውን ቃለ ምልልስ እነሆ፡-

የመጨረሻውን የማራቶን ውድድር የት ነው የምትሮጠው?
ተው እባክህ … አሁን ማራቶን ኢንቨስትመንት ሆኗል፡፡
የመጀመሪያውን የገንዘብ ሽልማት የት ነው የተቀበልከው?
በ1984 ዓ.ም ይመስለኛል፡፡ ጃፓን ውስጥ በኢኬደን በተደረገው የማራቶን ዱላ ቅብብል ላይ ነው፡፡ በቡድን ሁለተኛ ወጥተን ለሽልማት በቅተናል፡፡ ከእነ ሙሉ አበሉ 960 ዶላር ደርሶኛል፡፡
በአትሌቲክስ በተለይ በማራቶንና በጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች የተመዘገቡ ውጤቶችና የተበረከቱ ሽልማቶችን በዝርዝር የሚያወጣ ድረገፅ አለ፡፡ እዚያ ላይ እንዳየሁት፤ በአትሌቶች  የገንዘብ ሽልማት አንተ ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማግኘት ከዓለም አትሌቶች በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠሃል፡፡ ልክ ነው?
ልክ ሊሆን ይችላል፡፡ የገንዘቡን ነገር እኔም እንኳን አላውቀውም፡፡ ብሩ ይመጣል - ይሄዳል፤ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ባገኘህ ቁጥር ቀዳዳው ይበዛል፡፡ የሚባለውን ያህል አግኝተሃል ወይ? ብትለኝ… አሁን በኪሴ እንኳን  በዶላር በብርም የለም፡፡ ገንዘቡ ሙሉ በሙሉ ኢንቨስትመንት ላይ ነው ያለው፡፡ በእርግጥ በሩጫው ብዙ ዓመት ቆይቻለሁ፡፡ 23 ዓመት አካባቢ ነው፡፡ በአትሌቲክስ ይህን ያህል ዓመት የሩጫ ዘመን ያሳለፈ በአጭርም ሆነ በረዥም ርቀት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባትም በስፖርቱ ለረጅም አመታት በመቆየት የእኔ ክብረወሰን ሳይሆን አይቀርም፡፡
ወደ ኢንቨስትመንት የገባኸው ገና በስፖርቱ ውስጥ እያለህ ነበር፡፡ ለመሆኑ ማንን አርአያ አድርገህ ነው?
ማንንም አይቼ አይደለም ወደ ኢንቨስትመንቱ የገባሁት፤ በራሴ ተነሳሽነት ነው፡፡ ዋናው ወደ ኢንቨስትመንቱ እንድቀላቀል ያደረገኝ በውጭ ሀገራት የማያቸው ነገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖሩ ብዬ እመኝ ስለነበር ነው፡፡ ፎቆችን …ሌሎች ነገሮችንም ስመለከት፣ የተመለከትኩትን ለኢትዮጵያ እመኝ ነበረ፡፡ ከዚያ የመጀመሪያውን ህንፃ ስንሰራ… ቀስ እያልን ሁለተኛውን ህንፃ ስንሰራ… ልክ የሆነ ደረጃ ላይ ስደርስ ወደ ቢዝነስ ማደግ እንዳለበት አሰብኩ፡፡ ምክንያቱም፤ ብዙ ገንዘብ ባገኘህ ቁጥር  ቢዝነስ ይኖርሃል፤ ቢዝነሱን ታሰፋለህ፤ ይህ ማለት ደግሞ ብዙ ሰዎችን ታሳትፋለህና ሰፊ እና ትልቅ ነገር ይፈጠራል ማለት ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት “ኃይሌ ዓለም ኢንተርናሽናል” በጣም ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ ከእህት ኩባንያው “ከማራቶን ኢንጅነሪንግ” ጋር አጠቃላይ ከ1600 ያላነሱ ቋሚ ሰራተኞች ያስተዳድራል፡
መጨረሻ የገባሁበት የቡና ኢንቨስትመንት ውስጥ 500 ሰራተኞች ገደማ አሉ፡፡ እነሱን… ቋሚ ለማለት ያስቸግራል፡፡ እኛ ሁሉንም ሰራተኞቹን ዓመቱን ሙሉ ነው የምንይዛቸው፤ አንዳንዶቹ ግን አንድ ወር ሁለት ወር ይሰሩና ይወጣሉ፡፡ ሌላ ግሩፕ ደግሞ ታመጣለህ… ለምሳሌ፡- ዘንድሮ ቡናውን ለመትከልና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን 500 ሰው ያስፈልገናል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ቡና ለቀማ ስንገባ ደሞ ከ1000 ሰው በላይ ያስፈልገናል፡፡ 1500 ሔክታር መሬት ስፋትን በማልማት ላይ ነው የምንገኘው፡፡
እንዴት ነው ወደ ቡና ኢንቨስትመንት ገባኸው?
ወደ ቡና ሥራ ስንገባ፣ ኢትዮጵያ ምንድን ነው የሚያስፈልጋት የሚለውን አገናዝቤ ነው፡፡ ለሀገር የሚሆን ቀጣይነት ያለው ቢዝነስ ይሆናል በሚል እምነት፡፡ የቡና ምርትን ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ኤክስፖርት ማድረግ አለባት፡፡ በቡና ዙርያ አንድ ያስቸገረን ነገር ምን መሰለህ? በደቡብ ክልል የቡና ኢንቨስትመንቱን በጀመርንበት በማሻ ምንም አይነት መሰረተ-ልማት የለም ማለት ይቻላል፤ በጣም ተቸግሬ ነው የተመለስኩት፡፡ እስከ ሚዛን ተፈሪ ያለው መንገድ እየተሰራ ነው፡፡ ከሚዛን ተፈሪ እስከ ማሻ ያለው ወደ 150 ኪ.ሜ የሚደርሰው መንገድ ግን መንገድ ተብሎ ሊጠራ የሚችል አይደለም፡፡ ትልቁ ስጋቴና እንደ ችግር የማነሳው እዚያ የተከልነው ቡና ከዓመት በኋላ ይደርሳል፡፡ እንዴት ነው ይዘነው የምንወጣው? እኛ ወደ ማሻ የሚያስገባ 15 ኪ.ሜ መንገድ እየሰራን ነው፡፡ የቡናውን ስራ ስንጀምር “አብደሃል እንዴ እዚህ ገብተህ የምትጀምረው?” ተብዬ ነበር፡፡ ወደ ውስጥ የሚገባው በፈረስ ነው፤ ሰራተኞቹ መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው ያሉት፡፡ እኔም መስዋዕትነት እየከፈልኩ ነው ያለሁት፡፡ ግን ነገ የሚመጣው ነገር አይታወቅም፡፡  
 በአጠቃላይ የኢንቨስትመንት እድሉ ካለ፤ መሰረተ - ልማቱ በተለይ በገጠር ከተሞች በደንብ ተጠናክሮ ቢስፋፋ  ደስ ይለኛል፡፡ አሁን ማሻ  ውስጥ ትልቅ የተፈጥሮ ሃብት አለ፡፡ ቡናው፣ ማሩ፣ የእንስሳት ተዋፅኦው፡፡ ይገርምሃል… ቁጥር አንድ የኢትዮጵያ ማር ያለው ማሻ ላይ ነው፡፡ እና እነዚህ ነገሮች ታሳቢ ተደርገው መንግስት መሰረተ ልማቱን ቢያስፋፋ ጥሩ ነው፡፡
የኢንቨስትመንት መነሻህ ምንድን ነው?
የመጀመሪያው ኢንቨስትመንቴ ፎቅ ቤት ነው፡፡ ከአቴንስ ስመለስ መንግስት 450 ስኩዌር ሜትር ቦታ ሸልሞኝ ነበር፡፡ እዚያች ቦታ ላይ ባለሁለት ፎቅ ህንፃ ሰራሁ፡፡ ፎቁን የዛምቢያ ቻንስለር ተከራየው፡፡ ሰፈሩ የድሮው ኤርፖርት አካባቢ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲያውኑ ትንሽ ተለቅ ያለ ነገር መስራት አለብኝ ብዬ ወሰንኩኝ፡፡ ኡራኤል አካባቢ ዓለም ህንፃን ሰራን፡፡ ከእነ ሰንሻይን፣ ለገሰ ዋሪት ጋር አምስት ሰዎች ነበርን፡፡ እንደውም ፎቅ ሰርቶ በማከራየት የመጀመሪያዎቹ ሳንሆን አንቀርም፡፡ የአከራይ ተከራይ ንግድ እንደ ኢንቨስትመንት እንዲቆጠር፤ በጊዜው ወደ ንግድ ምክር ቤት የሄድነው ከአምስት የማንበልጥ ሰዎች ነበርን፡፡ ድሮ የአከራይ ተከራይ አሰራር እንደ ንግድ አይታይም ነበር፡፡ ህንፃ እንደ አንድ የንግድ ዘርፍ እንዲያዝ ያደረግነው እኛ ነን፡፡ ያንን ካደረግን በኋላ ወደ ክፍለ ሀገር ሄድንና ወደ ሁለተኛው አይነት የኢንቨስትመንት መስክ ገባን፡፡ ይህም ለእናቴ መታሰቢያነት ባህርዳር የከፈትነው ት/ቤት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመለስን፡፡ ሌላ ህንፃ ገነባን፡፡ በመቀጠል ደግሞ ወደ አሰላ ተመለስን፤ ት/ቤትና ህንፃ ሰራን፡፡ ደግሞ ወደ ናዝሬት ሔድን፤ አነስ ያለች ህንፃ ሰራን፡፡ ከዚያ እያሰፋን ስንሄድ ወደ ሆቴል ኢንቨስትመንት ገባን፡፡ ሀዋሳ የሚገኘውን “ኃይሌ ሪዞርት”ን ሰራን፡፡ ለምሳሌ፤ ኃይሌ ሪዞርት ብዬ ስሰይም ስሙ ራሱ ብራንድ አለው፡፡ ግን ጉዳትም ነበረው፤ “ኃይሌ” ተብሎ ሆቴሉ ሲሰየም ሰው የገመተው ነገር በዛና ሆቴሉ አነሰበት፤ ሰርቪሱም ጥሩ አልነበረም፡፡ በግንባታ ወቅት የነበሩትን ሰዎች ነው አሰልጥነን ወደ ሆቴል አገልግሎት ያስገባናቸው፡፡ እና ብዙ እቃ አለቀ፤ ብዙ ነገር ሆነ፤ አሁን ግን ብቁ ናቸው፡፡
እነዚያን ሁሉ ህንፃዎች ስትገነባ ገና በሩጫው ወርቃማ ዘመንህ ላይ ነበርክ፡፡ ሁለቱን አጣጥሞ መምራት አልከበደህም?
አዎ እንዳልከው ያን ግዜ ብዙ የምለማመድበትና የምሮጥበት ጊዜ ነበር፡፡ እንደውም ያኔ አንድ የሚቀለድብኝ ቀልድ ነበረ፤ ምን ይባል ነበር መሰለህ፡- ‹‹የኃይሌ አርክቴክት፣ ኃይሌ አንድ ሩጫ ሲያሸነፍ አንድ ህንፃ ጨምርበት ይለዋል›› እያሉ ያሾፉብኝ ነበር፡፡ በወቅቱ ትኩረቴ ሩጫው ላይ ስለሆነ ኮንስትራክሽኑን የሚመራው አሰፋ የተባለው ታላቅ ወንድሜ ነበር፡፡ አንድ የሚገባኝ ነገር ምን መሰለህ… ሩጫ ማለት ሁልጊዜ የምትሰራው ስራ አይደለም፤ አንድ ቀን እንደሚቆም ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፤ እንደውም እኔ እድለኛ ነኝ፤ ለረዥም ጊዜ ቆይቻለሁ፡፡ ይህ ቆይታዬም ለኢንቨስትመንቱም ብዙ አስተዋፅዖ አድርጎልኛል፡፡
ፎቅ ሰርቶ በማከራየት ፈር ቀዳጅ እንደነበራችሁ ነግረሃኛል፡፡ እስቲ ሌሎች ፈርቀዳጅ ኢንቨስትመንቶች አሉህ?
ለምሳሌ፤ ሲኒማ ቤት በመክፈት የመጀመርያዎቹ እኛ ነበርን፡፡ የሲኒማ  ሀሳብ እንዴት መጣ መሰለህ? ቦሌ አካባቢ ከሚገኘው የኃይሌ ዓለም ህንፃ ጀርባ መሬት የነበራት አንድ ሴትዮ “እናንተ እዚህ ፎቅ ሰርታችሁ እኔ መኖርያ ቤቴን እዚህ አልሰራም” በማለት ሊዝ ቢሮ ሄዳ “ገንዘቤን መልሱልኝ” አለቻቸው፡፡ ከዚያ እሷ ካልፈለገች ብለን እኛ አመለከትንበት፤ ለሊዝ ቢሮው፡፡ በሷ ዋጋ ይሰጠን አልንና ተሰጠን፡፡ ዓለም ሲኒማን ገነባን፡፡ በጣም ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊ የሳውንድ ሲስተም አሟልተን ሰራነው፡፡ ስራ ሲጀምር ግን ፊልም ሊያይ የሚገባ ብዙ ሰው አልነበረም፡፡ በስራ ቀናት 4 ሰው፤ ቅዳሜና እሁድ ከሆነ ደግሞ 12 ሰው ይገባ ነበር፡፡ “እንደዚህ ከሆነ ፊልም ማሰራት አለብኝ” አልኩ፡፡ ይሄኔ አብርሃም የተባለ አንድ የፊልም ባለሙያ ፊልም መስራት እንደምፈልግ ሰምቶ፤ “ነፃ ትውልድ” የሚል ስክሪፕት ሰጠኝ፡፡ አንብቤው ወደድኩትና ስራው አልኩት፡፡ ወደ 100ሺ ብር ይፈጃል ሲለኝ “በቃ ይሰራና ይምጣ” አልኩኝ፡፡ ፊልሙ ተሰራ፤ ሰዎች ወደዱት፡፡
ከዚያ ሌሎች የአማርኛ ፊልሞች ወደ ሲኒማ ቤቱ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፣ ከመጡት ፊልሞች መሀል እነ “ቀዝቃዛ ወላፈን” ትዝ ይሉኛል፡፡
ሌላው በፈርቀዳጅ በመሆን ጀምረነዋል ብዬ የማስበው የጂም አገልግሎት ነው፡፡ ጂም ሰርቶ በአገልግሎት ሰጪ ኢንቨስትመንት መሰማራት ብዙም አይታወቅም ነበር፡፡ ስንጀምር ደንበኞቻችን በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡ ዛሬ ተጠቃሚው ብዙ ሆኗል፡፡
ሆቴል ሪዞርት በመስራትም ፈር የቀደድን ይመስለኛል፡፡ የሪዞርት ስራ ብዙ አልተለመደም ነበር፡፡ በወቅቱ በሆቴል ስራ ዘርፍ የሰለጠኑ ሰዎች በብዛት ባለመኖራቸውና ሙያውም ያን ያህል ያልተለመደ ስለነበር “ሃይሌ ሪዞርትን” ገንብተን ወደ ስራ ስንገባ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ ሪዞርቶች በዝተዋል፡፡ የሆቴል ኢንቨስትመንት በመስፋፋቱና ባለሙያዎች በመበርከታቸው ብዙ ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡
ከሌላው ዓለም አትሌቶች በተለየ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በብዛት በቢዝነስ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በሌሎች አገራት እውቅናና ዝና ያላቸው አትሌቶች ስፖርቱን ሲያቆሙ ባጠራቀሙት ገንዘብ የተንደላቀቀ ህይወት ይመራሉ እንጂ እምብዛም ቢዝነስ ላይ አይሰማሩም፡፡ የእኛዎቹ እንዴት ቢዝነስ ላይ ሊያተኩሩ ቻሉ?
አዲሱ ትውልድ ካለፈው እየተማረ፣ ስፖርቱን ባቆም በምን እተዳደራለሁ? ብሎ እያሰበ ይመስለኛል፡፡ በስፖርቱ ዓለም ውጤታማ ከነበሩት ጥሩ ልምዳቸውን ትቀስማለህ፡፡ ገንዘብ ካገኘህ በኋላ ያገኘኸው ገንዘብ ይጠፋል - ያልቃል፡፡ ስለዚህ፤  ገንዘቡ ሌላ ገንዘብ መውለድ መቻል አለበት፡፡ እንደዚህ ነው  እኔ የማስበው፡፡ አንድ ስለ ንግድ ያነበብኩትን ልንገርህ፡- መሬት ግዛ፤ ምክንያቱም የሚፈበረክ ነገር አይደለም ይላል፡፡ እሱ ላይ ነው መጀመሪያ ትኩረቴን ያደረግሁት፤ መሬት ብቻውን ገዝቶ ማስቀመጥ አይደለም መገንባት ነው፡፡ ከዚያ ተሻጋሪ ንብረት ይሆናል ማለት ነው፡፡
የውጪውን ተመክሮ ስትመለከት… ለምሳሌ አሜሪካ ወይም ኬንያ ብዙዎቹ በስፖርት ዓለም ውስጥ የነበሩ ሰዎች መጨረሻ ላይ ለራሳቸው መሆን አቅቷቸው ይቸገራሉ፡፡ ምክንያቱም፤ ዝነኛና ውጤታማ በነበሩባቸው ጊዜያት አባከኝ ነበሩ፡፡ ስፖርቱ ሲቆም ገቢው ይቆማል፣ የነሱ አባካኝነት ግን ይቀጥላል፡፡ በአብዛኛው ይህንን ችግር በኬንያ አትሌቶች ላይ አስተውላለሁ፡፡  በኬንያ የቢዝነስ ፉክክሩም በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ወደኛ ስትመጣ፤ የኛ አትሌቶች በጣም እየጐበዙ መጥተዋል፡፡ የሚያገኙትን ገንዘብ ጥሩ ቦታ ያውሉታል፡፡ በተለይ ባለፉት 20 ዓመታት የተፈጠሩ ሯጮች ቢያንስ ገቢ አላቸው፡፡ እራሳቸውን ይችላሉ፤ ሰው የሚያስቸግሩ አይደሉም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ያልተሳካላቸው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኔ ሁሌ ጥሩ ምሳሌ አድርጌ የማነሳው አትሌት ወርቁ ቢቂላን ነው፡፡ ብዙ ብር አላገኘም፡፡ እንደማስታውሰው የዛሬ 20 ዓመት ዙሪክ ላይ ለእኔ አሯሯጭ ሆኖ እንዲቀጠር ሳደርግ ያስከፈልኩት ትልቅ ብር ነበር፡፡ ዛሬ ወርቁ ቢቂላ ከ100 በላይ ሰራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ ሁልጊዜ እንደ ምሳሌ አነሳዋለሁ፡፡ ቁምነገሩ፤ ብዙ ገንዘብ ማግኘት አደለም፤ ያለውን ገንዘብ በጥሩ ቦታ ማዋል ነው፡፡
ሌሎች አትሌቶች ካንተ የተማሩ ይመስልሃል? አርአያ ሆኛቸዋለሁ ብለህ ታስባለህ?
በየቤቱ እየሄድክ እንደዚህ አድርጉ፣ እንዲህ አታድርጉ፤ ልትል አትችልም፡፡ ነገር ግን አንድ የሚታይ ነገር ስትሰራ ራሳቸው ካንተ ይማራሉ፡፡ ወጣቱ እንደውም እያሻሻለው ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ በቡና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት የተነሳሳሁት ከበላይ ወለሼ ተመልክቼ ነው፡፡ እሱ ወደዚህ ኢንቨስትመንት ሲገባ ያገኘውን ተመክሮ መነሻ በማድረግ ነው የገባሁበት፡፡ ሌላው ደግሞ ከኔ ይማራል፡፡ ለምሳሌ እኔ የሚቀጥለውን ቡና አብቃይ፣ ለመንገድ ቀረብ ያለ ቦታ እንዲመርጥ እመክረዋለሁ፡፡ ምክንያቱም መንገድ በሌለበት መስራት በጣም ከባድ ነው፡፡ መንገድ በመንግስት እንጂ በግለሰብ ደረጃ መስራት ያስቸግራል፡፡
ከአትሌቶች ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች በኢንቨስትመንት ዙርያ እንመካከራለን፤ ሃሳብ እንለዋወጣለን፡፡ ግን ለማንም ምንም የተለየ ድጋፍ አላደረግሁም፡፡ እንዳልከው የኔ ኢንቨስትመንት ትንሽ ሰፋ ያለ ነው፤ ትምህርት አለው፣ አገልግሎት አለው፣ ምርት አለው፡፡ በአሰላ እና ባህር ዳር በሚገኙ ት/ቤቶች ውስጥ ከ3ሺህ  በላይ ተማሪዎች አሉን፡፡ እነዚህ ት/ቤቶች ስኬታማ በሚሆኑበት አቅጣጫ አስፋፍተናቸዋል፡፡ አሁን በባህር ዳር ትምህርት ቤት ፕሪፓራቶሪ ጀመርናል፡፡ ላብራቶሪ እና ኮምፒውተር ክላስ አለው፡፡ በት/ቤቶች ኢንቨስትመንት ላይ የማገኘውን እርካታ የትም የማገኘው አይደለም፡፡ በመጀመሪያው ዙር ከእኛ የጨረሱ ልጆች አሁን ሁለተኛ ዓመት የሜዲካል ተማሪዎች መሆናቸውን ስሰማ በጣም ኮርቻለሁ፡፡ ለአንድ አገር ንቁ ትውልድን ማፍራት መቻልን በራሱ እንደ ትልቅ ኢንቨስትመንት ውጤት ማየት ይቻላል፡፡
የመንግስት ካሪኩለም እያከበርን በራሳችንም የምንሰራባቸው አቅጣጫዎች አሉ፡፡ ተማሪዎቻችን ጠንከር እንዲሉ በማሰብ የማስተማርያ ዘዴያችንን የቀረፅነው የህንድን ሞዴል አድርገን ነው፡፡ ይህ የትምህርት አሰጣጥ  ደግሞ ልጆቹን ረድቷቸዋል፡፡ ይህንን ት/ቤት ከከፈትን 14 ዓመት ሆኖናል፡፡ እስካሁን ምንም አይነት ሳንቲም ወደ ኪሴ አልገባም፡፡ እንደውም በመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት ት/ቤቱ በኪሳራ ነበር የሚሰራው፡፡ ነገር ግን እርካታ ይሰጠኛል፤ ልጆቹ ጥሩ ቦታ ደርሰው ማየት በራሱ ትልቅ ትርፍ ነው፡፡
በቢዝነስ ውጤታማ ለመሆን ምን ያስፈልጋል ትላለህ?
መስራት አለብን፤ እድገትን የምንፈልግ ከሆነ እንደ ባለሀብት ሳይሆን እንደ ሰራተኛ ሆነን መስራት አለብን፡፡ በምንሰራው ስራም አርአያ መሆን መቻል አለብን፡፡ ፈተናዎችን መጥላት የለብንም፡፡ ሌላው ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ብቻ አይደለም መስራት ያለብን፡፡
በሆቴል ዘርፍ ከአንድ ተነስተን 4 ደርሰናል፡፡ ዝዋይ ላይ ከሆቴሉ አጠገብ ሌላ መሬት ገዝተን አስፋፍተናል፡፡ “ኃይሌ ሪዞርት” አዋሳ፣ “ኃይሌ ሆቴል” ሻሸመኔ፣ ኃይሌ ሪዞርት ዝዋይ (አሁን ባቱ ነው የሚባለው)፡፡ ጂም ስንጀምር ደግሞ ቦሌ ጀመርን መገናኛ ቀጠልን፡፡ አሁን ደግሞ የመዋኛ ስፍራ ያለው ኡራኤል ላይ ከፍተናል፡፡ በአንድ ጊዜ ከመቶ ሰው በላይ የሚያስተናግድ ጂም እስከመክፈት ደርሰናል፡፡ በሪል እስቴቱ ደግሞ ወደ 120 ኮንዶሚኒየም፣ 31 የሚደርሱ ግራውንድ ፕላስ ዋን ቪላዎች ገንብተን ጨርሰናል፡፡ ሀያት አካባቢ ነው የተገነቡት፡፡ አሁን ግን ከሪል እስቴቱ እየወጣን ነው፡፡ ምክንያቱም ቀላልና አትራፊ ቢዝነስ ስለሚመስል ብዙ ሰው ገብቶበታል፡፡ የሪል እስቴት ባህሪ እንደሌሎቹ ቢዝነሶች ቀስ እያለ እየተዳከመ አይደለም የሚሄደው፤ በአንዴ ነው ኪሳራ ውስጥ የሚከትህ፡፡ የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ አይተናል፡- አሜሪካንና አውሮፓን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንግሊዝ አምና እና ካቻምና ተመልክቻለሁ፤ 5 ሚሊዮን ፓውንድ የነበረውን ሆቴል 1 ሚሊዮን ፓውንድ የሚገዛው ሲጠፋ ስታይ ትደነግጣለህ፡፡ ስለዚህ፤ አሁን፤  የሪል እስቴት ግንባታ አቁመናል፡፡ ምክንያቱም፤ ገንዘብ እየያዘብን ነው፡፡ አሁን ትኩረታችን ሆቴሉና ቡናው ላይ ነው፡፡
ማዕድን ደግሞ ሌላው በቅርቡ የገባንበት የኢንቨስትመንት መስክ ነው፡፡ ያተኮርነው የወርቅ ማእድን ፍለጋ ላይ ነው፡፡  እሱ ደግሞ ሌላው አስቸጋሪና ከባዱ ነገር ነው፡፡ ደቡብ ክልል ውስጥ “አሮሬሳ” ወይም “ግርጊያ” አካባቢ ነው የምንሰራው፡፡ የምንሞክራቸው ነገሮች ብዙ ያልተሞከሩ ወይም ደግሞ ቀደም ብለው በመንግስት ሲሰሩ የነበሩ ናቸው፡፡
የኃይሌ ዓለም ኢንተርናሽናል እህት ኩባንያ ስለሆነው ስለማራቶን ኢንጂነሪንግ ንገረኝ…
ማራቶን ሞተር ኢንጂነሪነግን ከመክፈታችን በፊት ከመኪኖች ማምጣት ጋር የተያያዘ ኢንቨስትመንት የማላውቀው ቢዝነስ ነበር፡፡ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነን ነው ያቋቋምነው፡፡ የኮርያ መኪናዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም የታወቁ ናቸው፡፡ በእኛ አገር ግን ብዙ ሰው የተሰማራበት አልነበረም፡፡ ለምሳሌ፤ ሀዩንዳይ  የሚባለው የመኪና ምርት ብዙም አይታወቅም ነበር፡፡ ይህን አገናዝበን ከኮርያ ባለሃብቶች ጋር ለመስራት ጥያቄ አቅርቤ ፍቃደኛ ሲሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ አብሮኝ ሊሰራ የሚችል ሰው አጣሁ፡፡ በኋላ ሞይንኮ የሚሰራ ጓደኛ ስለነበረኝ እሱን ስጠይቀው፤ “አንተ ስም ስላለህ ሊሳካ የሚችል ኢንቨስትመንት ነው” ብሎ ስራ ጀመርን፡፡ ዛሬ “ማራቶን ሞተር  ኢንጅነሪንግ” እጅግ ስኬታማ ሆኗል፡፡
“ማራቶን ሞተር ኢንጅነሪንግ” የሃዩንዳይ መኪና ምርቶችን አምጥቶ የሚሸጥ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱን የሚመራው ስራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ፣ በመስኩ የረዥም ጊዜ ልምድ ያለው ስለሆነ፣ ውጤታማ ስራ እየሰራ ነው፡፡ የማራቶን ሞተር ኢንጅነሪንግ ካፒታል ወደ 70 ሚሊየን ብር ገደማ ደርሷል፡፡
የኃይሌ ዓለም ኢንተርናሽናልና የእህት ኩባንያው የማራቶን ሞተር ኢንጅነሪንግ ካፒታል ከቢሊዮን ብር አላለፈም እንዴ?
አይሂሂሂ… አዎ ምናልባት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል፡፡ ሆቴሎቹ በራሳቸው ቀላል ካፒታል የሚጠይቁ ኢንቨስትመንቶች አይደሉም፡፡
አሁን ሩጫውን በማቆም ላይ ነህ፤ ከቢዝነስ ዘርፉ ያንተ ሚና ምንድን ነው?
“ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል”ን የምንመራው እኔና ባለቤቴ ነን፡፡ እኔ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪጅ ነኝ፡፡ አለም ምክትል ነች፡፡ ሌሎች ሁለት ማኔጂንግ ዳይሬክተሮች አሉ፤ ከሥር ሌሎች ማናጀሮች አሏቸው፡፡ ት/ቤቶቹን የሚያስተዳድሩ ዳይሬክተሮች አሉ፡፡ ሆቴሉ፣ ሪል እስቴቱ እና ጂሙ በአንድ ዳይሬክተር የሚመሩ ናቸው፡፡ እኔ ደግሞ ከላይ ሆኜ ታች ድረስ ወርጄ እሰራለሁ፡፡
ለምሳሌ ሀዋሳ ባለው የኃይሌ ሪዞርት አትክልት እንዲተከል እናገራለሁ፤ ዳይሬክተሩ ለማናጀሩ እንደ አግባብነቱ በመንገር ያሰራል፡፡ ይህ ብቻውን አያረካኝም፡፡ እኔ ዶማውን አንስቼ አትክልቱን ይዤ፣ አትክልተኛውን በዚህ መልኩ ስራ ብዬ አሳየዋለሁ፡፡ በሁሉም የኢንቨስትመንት መስኮች ሰርቶ የማሰራት ፍልፍስናን እከተላለሁ፡፡ ውጤቱንም አይቼዋለሁ፤ ሰራተኞቼ ከኔ ጋር መስራት ያስደስታቸዋል፡፡
ኩባንያዎችን የማስተዳደርና የመምራት ብቃት ያዳበርከው እንዴት ነው?
የተለያዩ የቢዝነስና የማኔጅመንት መፃህፍቶችን አነባለሁ፡፡ ጋዜጣም አያመልጠኝም፡፡ ከሰው ምክር እጠይቃለሁ፡፡ ያገኘሁትንም ምክር በአግባቡ እረዳለሁ፡፡ እኔ እነ ማይክሮ ሶፍት… እነ “አፕል” የሄዱበትን አይነት መንገድ ለመሄድ አልችልም፡፡ በእነሱያ አይነት ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ከፍተኛ የፈጠራ ተሰጥኦ ያስፈልጋል፡፡ የራሴ የሆነ ፈጠራ ሊኖረኝ ይገባል፡፡ ስለዚህ፤ ከእነሱ በተለየ እንደ አርዓያ የምትከተላቸው ሰዎች አሉኝ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ በቀለ ሞላ የኔ ሮል ሞዴል (አርአያ) ነው፡፡ በቀለ ሞላ፤ የፍራንቻይዝ አሰራር በማይታወቅበት ዘመን በመላው አገሪቱ ሆቴሎችን ያስፋፋ ታላቅ ሰው ነው፡፡
ወደፊትስ በኢንቨስትመንቱ ልታስፋፋ ያሰብካቸው ነገሮች አሉ? አዲስ የኢንቨስትምንት ሀሳብ…
የሆቴል ዘርፉን ማስፋፋት እፈልጋለሁ፡፡ አዲስ አበባ ላይ ከሰራሁ ሰፋ ያለ ነገር ነው የምሰራው፡፡ ሌላው ወደ አርባ ምንጭ መሄድ እፈልጋለሁ፡፡ የቱሪዝም መዳረሻ በሆኑት አካባቢዎች ላይ ለመስራት እቅድ አለኝ፡፡ ቢዝነስ ስትሰራ ሁልጊዜ የት ነው የሚያዋጣው? ብለህ ማሰብ አለብህ፡፡ ዝም ተብሎ አይሰራም፡፡ ቢዝነስ ለውጥ የማያመጣ ከሆነ አልሰራውም፤ ምክንያቱም መጀመሪያ ራሴ ልጠቀም ነው የምሰራው፤ እኔን ካልጠቀመ፣ ሰውን ካልጠቀመ፣ ሀገርን ካልጠቀመ ለምን እሰራለሁ? በኢንቨስትመንት ዘርፍ ስሰማራ ሁለት ነገሮችን አስልቼ ነው፡፡ የመጀመርያው ምን ያህል እርካታ ይሰጠኛል? … ሌላው የትኛው ገንዘብ ያመጣልኛል? የሚለው ነው፡፡ አንድ ቢዝነስ የፈለገ ትርፍ ቢኖረው እንኳን እርካታ ከሌለው ዋጋ የለውም፡፡
ታላቁ ሩጫ እንደ ኢንቨስትመንት ይቆጠራል?
ታላቁ ሩጫ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ከአፍሪካ አንደኛ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ሩጫ ደቡብ አፍሪካ እንኳን አላዘጋጀችም፡፡ ናይጄሪያም አንዴ ሞክራ አልተሳካም፡፡ ሰው ከየት እንደሚነሳ የት እንደሚቆም አያውቀውም፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ስንጀምረው ብዙ ብር እያከሰረን ነበር፡፡ አሁን ግን በንግድ ስር ተመዝግቦ ማትረፍ ጀምሯል፡፡ ተአምራዊ ስራ እየተሰራበት ነው፡፡
ዛሬ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች በርካታ ስፖርተኞችን በማሳተፍ፤ ጠቃሚ አገራዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍ፤ ከበርካታ አገር ድርጅቶች ጋር በመስራት እና የአገር ገፅታን በመገንባት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተጋበዙ ውድድሮችን እያዘጋጁ ናቸው፡፡ አሁን የኛ ልጆች በቅርብ እንኳን የህንድ ግማሽ ማራቶን አዘጋጅተዋል፡፡
ከአትሌቲክስ ጋር በተያያዘ የጀመርካቸው ኢንቨስትመንቶች የሉም?
ኢትዮጵያ ውስጥ  በስፖርት ትርፍ አትርፈህ መስራት ኀጥያት ነው፡፡ “እንዴት ከስፖርት ታተርፋለህ” ትባላለህ፡፡ ግን ትልቁ ትርፍ ያለው እዚያ ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን፤ የአትሌቲክስ ህግ ቢኖረን… ከገጠር ምን አይነት ሰው እንደማመጣ አውቃለሁ፤ ከዚያ በዘርፉ አብቅቼው ይሄንን ያህል ፐርሰንት ትሰጠኛለህ ብዬ ውል አስገባና… መስራት ይቻላል፡፡ ግን በቃ ህጉ የለም፡፡ ብዙ ጊዜ የተነጋገርንበት ጉዳይ ነው ከድሮዎቹ የኮሚሽኑ አመራሮች ጀምሮ እስካሁን ድረስ፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ለየት ያለ ነገር በጣም ነውር ነው፡፡ ለዚያ ነው ኳሱም ሌላውም ውጤታማ ያልሆነው፡፡ ከመጀመርያ አንስቶ ማሳደግ…. ማብቃት ከዛም ለውጤት ማብቃት ይፈልጋል፡፡ ይሄ አለም እየተከተለችው ያለው አሰራር ነው፣ እኛ ጋ ግን የተፃፈ ህግ የለም፡፡ እስከዛሬ የመንግስት ድርጅቶች ናቸው ሙሉ በሙሉ ስፖርቱን የያዙት፤ በግል የተቋቋመ ክለብ የለም፡፡ ሐረር ቢራ ለግል ሲሸጥ እኮ ክለቡ ተበተነ፡፡ ስፖርት ኮሚሽን ፖሊሲ መቅረፅ አለበት፡፡ ለዚያ ደሞ የአለምን አሰራር ማየትና መፈተሽ አለብን፡፡ ለምሳሌ ኬንያ ካምፕ አለ፡፡ በየቦታው እነ ናይክ እና የመሳሰሉት የሚያሰለጥኗቸው ልጆች አሉ፡፡ እዚህ ካምፕ ይሰራ ሲባል አይቻልም፤ ምክንያቱም ህጉ አይፈቅድም፡፡

Monday, 09 March 2015 12:01

የፖለቲካ ጥግ

መንግሥት ሲሳሳት ትክክል መሆን አደገኛ ነው፡፡
ቮልቴር
እኔ የማውቀው ማርክሲስት አለመሆኔን ነው፡፡
ካርል ማርክስ
ነፃነት ማለት ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛው ሰው የሚፈራው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፤ አንዳንድ እንስሳት ግን የበለጠ እኩል ናቸው፡፡
ጆርጅ ኦርዌል
(Animal Farm)
ሁሉም አንድ ዓይነት የሚያስብ ከሆነ፣ የማያስቡ ሰዎች አሉ ማለት ነው፡፡
ጀነራል ጆርጅ ፓቶን
ነፃነት መውደድ ሌሎችን መውደድ ነው፣ ሥልጣንን መውደድ ራሳችንን መውደድ ነው፡፡
ዊሊያም ሃዝሊት
ሰዎች የንግግር ነፃነትን የሚጠይቁት ተጠቅመውበት ለማያውቁት የሃሳብ ነፃነት ማካካሻ ነው፡፡
ሶረን ኪርክጋርድ
ፖለቲከኛ የሚናገረውን ፈፅሞ ስለማያምን፣ ሌሎች ቃሉን እንዲጠብቅ መፈለጋቸው ያስገርመዋል፡፡
ቻርልስ ደጎል
ሙታን ለፍትህ ሊጮሁ አይችሉም፤ ያንን ማድረግ የህያዋን ኃላፊነት ነው፡፡
ሎይስ ማክማስተር ቡጆልድ

ከበደ ሚካኤል
(አዝማሪና ውሃ ሙላት)
   አንዳንድ ዕውነተኛ ታሪክ ሲቆይ ተረት ይሆናል፡፡ የሚከተለው ተረት የዚያ ዓይነት ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ የአማርኛ መምህር ስለግጥም አስተማሩና
“ቆቅ በሚለው ቃል አንድ ግጥም ፃፉ”
አሉና የክፍል ሥራ ሰጡ፡፡
አንድ ሁልጊዜ የሆነ ያልሆነ ጥያቄ እየጠየቀ የሚያስቸግራቸው ተማሪ አለ፡፡ ይህ ተማሪ እምብዛም አማርኛ የማይሳካለት ነው፡፡ በሌላ ትምህርት “ኤ” እያገኘ በአማርኛ ግን ይወድቃል፡፡ አማርኛ ክፍል ውስጥ መከራከሩን ደሞ ይቀጥላል፡፡ እልኸኛ ልጅ ነው፡፡ ለምሳሌ መምህሩ፤ “መተከዣ ምግብ ታውቃላችሁ?” ይላሉ፡፡ የሚመልስ ሲጠፋ፤ ራሳቸው ይመልሳሉ፡፡
“መተከዣ ምግብ ማለት እንደ ቆሎ፤ ቋንጣ፣ ዳቦ ቆሎ ወዘተ ያለ እየተጫወትን በዝግታ የምንበላው ነገር ነው” ይላሉ፡፡ ይሄኔ ያ ልጅ እጁን ያወጣል፡፡
“ዶሮ ወጥስ መተከዣ ምግብ አይሆንም?” ይላቸዋል፡፡
“አይ ዶሮ ለምሣ ወይ ለራት ርቦን በፍጥነት የምንበላው ነው፤ መተከዣ ምግብ አይደለም” ይላሉ፡፡
“ቀስ ብዬ ብበላውስ?” ብሎ ድርቅ ይልባቸዋል፡፡
“እንግዲያው የእኔ ልጅ ዶሮ ለአንተ…መተከዣ ምግብ… ይሁንልህ!” ይሉታል፡፡
ሌላ ቀን “ቅዳሜና እሁድን የት አሳለፋችሁ?” የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ፡፡
ያ ሞገደኛ ተማሪ እጁን ያወጣና፤
“ካምቦሎጆ” ይላል፡፡
“የመግቢያ ክፍያው ስንት ነበር?”
“አይ በከንቱ ነው የገባነው” ተማሪዎቹ ይስቃሉ፡፡
“በከንቱ አይባልም” ይላሉ የኔታ፡፡
“እሺ በባዶ?”
“በነፃ ብትል ይሻላል የኔ ልጅ”
“በዜሮስ ብለው?”
“ይሁንልህ” ይሉታል፡፡
ዛሬ እንግዲህ “ቆቅ” በሚለው ቃል ግጥም ግጠሙ ብለዋል - የኔታ፡፡ ሁሉም ተማሪ አንድ አንድ ስንኝ እየፃፈ ሰጠ፡፡ ያ ሞገደኛ ተማሪም ፅፎ ሰጥቷል፡፡
የኔታ አርመው ስም እየጠሩ መለሱ፡፡ ስምንት ከአሥር፣ ዘጠኝ ከአሥር ያገኙ አሉ፡፡
ያ ሞገደኛ ተማሪም ወረቀቱን ተቀበለ፡፡ ግን ማርክ አልተሰጠውም፡፡
“የኔታ፤ የእኔ ለምን አልታረመልኝም?” አለና ጠየቀ፡፡ እስቲ አንብበው የፃፍከውን ግጥም፡፡
ልጁ ማንበብ ጀመረ፡-
“ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ቆቅ
አፋፍ ለአፋፍ ስታሽሟቅቅ” ብሎ ጨረሰ፡፡
የኔታም “ማሽሟቀቅ” ምን ማለት ነው?” አሉና “ትርጉሙ ካልታወቀኮ ለግጥሙ ማርክ ለመስጠት አይቻልም” አሉት፡፡
“እሺ ላስረዳዎት፡፡ ማሽሟቀቅ ማለት በመንፏቀቅ ና በማሽሟጠጥ መካከል ያለ ነገር ነው”
“በል በል በል …አንድ ከአሥር አግኝተሃል፡፡ ይህም ለተማሪ ዜሮ ስለማይሰጥ ነው፡፡ ቅ እና ቅ መግጠሙን ማወቅህ ይበቃል” አሉት፡፡
*    *    *
በተሳሳተ ወይም በሌላ ቃል፤ አዋቂ ለመምሰል የሚጥሩ አያሌ ናቸው፡፡ ቃል ግን አይታበልም፡፡ አንዳንዴም ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለው “ቃል የዕምነት ዕዳ ነው”፡፡ ቃልን በትክክለኛ አግባቡ በቦታው ማስቀመጥ ጥንቃቄንና ታማኝነትን የሚጠይቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡
እነሆ አዲስ አድማስ ጋዜጣችን አሥራ አምስት አመት ሞላው፡፡ ገና ከጅምሩ፣ ገና ማለዳ፤ “እኛ ጋዜጣ ብቻ ሳንሆን ኃላፊነት የሚሰማው ሥነ ጽሑፍ ነን” ብለን ነበር፡፡
ኃላፊነታችንን መወጣታችንን”፤ አንባቢያችን ይመሰክራል፡፡
“ባህላዊ ጋዜጣ ነንም” ብለን ነበር፡፡ እስከዛሬ ከሰባት መቶ በላይ ተረቶችን በመፃፍ በባህላዊ ርዕሰ አንቀጽ አፃፃፍ ዘዴያችን ዘልቀናል፡፡ “የጥበብ መድረክ ነንም” ብለን ነበር፡፡ አያሌ ግጥሞችንና አጭር ልቦለዶችን አስነብበናል፡፡ “የእርሶና የቤተሰብዎ ጋዜጣ ነንም” ብለን ነበር፡፡
አያሌ አንባቢያን እጅ ገብተናል፡፡ ከነጭና ጥቁር ፅንፍ ይልቅ እመካከል ለሚገኘው ግራጫው ቦታ ላይ ያለ ሠፊ ማህበረሰብ እናግዛለን ብለንም ነበር፡፡ ያገለገልን ይመስለናል፡፡ “በአንፃራዊ መልኩ ሀሳብ ላለው ሁሉ የሃሳብ መስጫ መድረክ እንጂ የፖለቲካ አቋም ማራመጃ አይደለንም” ብለንም ነበር፡፡ ቃላችንን አክብረናል፡፡ ለእኛም ቃል የዕምነት ዕዳ ነበር፡፡ ነው፡፡ ነገም ሌላ ቃል ነው! ነገን ያየነው ገና ትላንትና ነው፡፡
የተመሠረትነው በዕውቀት ላይ ነው፡፡ ስለሆነም ስሜታዊነት አያጠቃንም፡፡ በማህበረሰባችን ውስጥ በትምህርት ማነስ የተፈጠረውን ገዋ (Vacuum) እንሞላለን የሚል ዕምነት አለን፡፡ ዓላማችን ኢንፎቴይመንት ነው፡፡ Infotainment የInformation እና የEntertainment ቅልቅል ነው - መረጃ መስጠትና ማዝናናትን የያዘ ፅንሰ ሀሳብ ነው፡፡ ባህል ላይ ተመሥርተን ፖለቲካን ልናስብ እንችላለን እንጂ ፖለቲካን እንደ ባህል አንወስደውም (We are culturally political and not politically cultural)
ከአንባቢዎቻችን ጋር ረዥም መንገድ ተጉዘናል፡፡ የጋዜጣ ሥራ በተለይ ባላደገ  አገር በወርቅ አልጋ በእርግብ ላባ ላይ የሚተኙበት አይደለም፡፡ ይህን አለማወቅ የዋህነት የሆነውን ያህል፣ አውቆ መደነባበርም የዚያኑ ያህል ሜዳው ገደል እንዲሆን የሚያደርግ አካሄድ ነው፡፡ “አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት” እንዲሉ፡፡ የተከፈተ በር አናንኳኳም፡፡ “አንኳኩ ይከፈትላችኋል” ስንባል ግን “አስቀድሞ ነገር ለምን ተዘጋ?” እንላለን፡፡
“እሾክ ብቻ ሆነ እግሬን ብዳብሰው
እንዴት መራመጃ መሄጃ ያጣል ሰው” ብለን በምሬት ብቻ አገራችንን አናጣም፡፡ ይልቁንም፤
“አገርህ ናት በቃ
አብረህ አንቀላፋ ወይ አብረሃት ንቃ!”
እንላለን፡፡ እኛ ብቻ አዋቂ የሚል ግብዝነት የለብንም፡፡ የብርሃን ነጠብጣብ ሁሉም ሰፈር አለ፡፡ በየት በኩል እናብራ ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ ተወርዋሪ ኮከብ እንዳለ ሁሉ ትልቁ ድብ እና ትንሹ ድብ አለ፡፡ የቡና ስባቱ መፋጀቱ ብንልም እንኳ፤ እንደ ቡና ከምንቀዘቅዝ (Decaffeination) እንደወይን አድረን ብንበስል (ብንመረቃ) እንመርጣለን፡፡ “ብልጥ ልጅ የያዘውን ይዞ ያለቅሳል” ብንልም፤ ለምን ያለቅሳል? ከማለት አንቆጠብም፡፡ ያልተመለሱ ዲሞክራሲያዊም ሆነ ሰብዓዊ ጥያቄዎችን እናስታውሳለን፡፡ የሕግ የበላይነት እከሌ ከእከሌ ሳይባል እንዲከበር እንወተውታለን፡፡ በምንም ሽፋን የሰው ልጅ እኩልነት እንዳይነካ መረጃዎችን ለመስጠት እንጥራለን…ትላንት እንዲያ ነበር፡፡ ዛሬም እንዲሁ ነው፡፡ ነገም ይቀጥላል፡፡
እነሆ! አሥራ አምስት ዓመታትን ተሻግረናል፡፡ በነዚህ ዓመታት ውስጥ የዛሬ አሥር ዓመት ትጉውን፣ ደጉን፣ ምሁሩን ሥራ አስኪያጃችንን (አቶ አሰፋ ጐሣዬን) አጥተናል፡፡ ምኔም እናስታውሰዋለን፡፡ ያልተዘመረለት ጀግና ነውና! ረቂቁን ሰዓሊና ገጣሚ መስፍን ሀብተማሪያምን፣ ሰፊ ማህበራዊ ዳሰሳን የተካነውን አብርሃም ረታንም አጥተናል፡፡ ነብሳቸውን ይማር!
እንደሌላው የህይወት መንገድ ሁሉ በጋዜጠኝነት ውጣ ውረድ ውስጥም ብዙዎች ይመጣሉ ብዙዎች ይሄዳሉ፡፡ በዚህ ውስጥ የመንግሥት ባለሥልጣናትም፣ ፓርቲዎችም፣ ታዋቂ ግለሰቦችም፣ ልዩ ልዩ ተቋማትም ወዘተ አሉ፡፡ ሁሎችም ይሰሙናል፤ ሁሉችም ከጥፋታቸው ይማራሉ ብለን አንጠብቅም፡፡ ለውጥ አድሮ አዳጊ ነው (incremental)፡፡ ዲሞክራሲም እንደዚያው፡፡ የብዙ ለውጦች እንቅፋት ጉራና ዝና ነው፡፡ ስለሆነም፡-
“ዝናኮ እንደንብ ነው
ዜማ አለው፣ ቃና አለው
መውጊያ እሾኩ ጉድ ነው!
የሰማያት ያለህ! ለካ ክንፍም አለው!”
የሚለውን ያልታወቀ ገጣሚ ፅሁፍ አበክረን እንገነዘባለን፡፡
በመጨረሻም ከደራሲ ከበደ ሚካኤል ጋር፤
“እስቲ ተመልከተው ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ
ተግሣፅም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ” ብንልም፤ በዚያ አናቆምም፡፡
“ምሥማር እንኳ ቢዘንብ፣ ከሰማይ ጣር ቁጣ
እንናገራለን፣ አድማጭ እስኪመጣ!” እንላለን፡፡
እስከዛሬ ላነበባችሁንና ነገም ለምታነቡን ምሥጋናችን ክቡርና የላቀ ነው!



Published in ርዕሰ አንቀፅ

ሁሌም ምርጫ ሲደርስ ብቅ ብቅ የሚሉ (በኢቢሲ ማለቴ ነው!) ፊታቸው “የቁጣ አስተማሪ” የሚመስል አንዳንድ ግለሰቦች አላጋጠማችሁም? ፖለቲከኞች ወይም ባለሥልጣናት እንዳይመስሏችሁ። (እነሱ አይቆጡም አልወጣኝም!) እነዚህኞቹን “የምርጫ ዬኔታ” ይሏቸዋል፡፡ ይሄ ስያሜ ለምን እንደተሰጣቸው አላውቅም፡፡ ምናልባት ቁጣ ቁጣ ስለሚላቸው ይሆን? የሚገርመው ደግሞ እየተቆጡ የሚያስተምሩን እንዴት ምርጫውን ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ---እንደምናደርገው ነው፡፡ (ሰላማዊ ምርጫ --- በቁጣ?!)
 እኔ የምለው ግን --- አንዳንድ ግለሰቦች “የቁጣ ፈቃድ” አላቸው እንዴ? ወይስ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል? ከምሬ እኮ ነው---መቼም አንድ ግለሰብ (ለብቻው) 90 ሚሊዮን ህዝብን ለመቆጣት የግድ ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ ፈቃድ ካለው ህግ አክባሪ ስለሆንን እንታገሰው ይሆናል፡፡ ያለዚያ ግን ---- (ምንም!!)  
በነገራችን ላይ ---- የህወሓትን 40ኛ ዓመት በዓል እንዴት አያችሁት? እንግዲህ በዓሉ ለአንድ ወር ያህል በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቶ ባለፈው እሁድ ተጠናቋል፡፡(አንድ ወር አላነሰችም?) የሸገር 125ኛ ዓመት የተከበረው እኮ ዓመቱን ሙሉ ነው (ዓመትም ተንዛዛ!) አንድ ነገር ልንገራችሁ--- የዘንድሮን ምርጫ ልዩ የሚያደርገው፣ የህወሐት 40ኛ ዓመት በተከበረ ማግስት በመዋሉ ነው፡፡ (የEBCን ዜና ቀማሁት አይደል!) አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ… የዘንድሮን የህወሐት በዓል ልዩ  የሚያደርገው ምንድን ነው ብትባሉስ? (ከ40ኛ ዓመቱ ውጭ ማለቴ ነው!) ቀላል እኮ ናት! (ሮኬት ሳይንስ አደረጋችሁት እኮ!) ልዩ የሚያደርገዋ---የህወሐት የቀድሞ ታጋዮች (አሁንማ ባለ ስልጣን ሆነዋል!) ከአርቲስቶች ጋር የሆድ የሆዳቸውን ማውራታቸው ነው!! (መሞዳሞድ ሌላ ነው!)
ተቃዋሚዎች በዓሉን አስመልክቶ የሰነዘሩት ትችት ግን አልገባኝም፤ “ኢህአዴግ በዓሉን ለምርጫ ቅስቀሳ ተጠቅሞበታል” ሲሉ ሰማሁ፡፡ (So what?) …ገና ለገና  በግንቦት ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ በየካቲት በዓል ላይከበር ነው? (“ማን ላይ ቁጭ ብለሽ ማንን ታምያለሽ” አሉ!) ከዚህም የባሰውን ደግሞ ልንገራችሁ፡፡ “የህወሐት በዓል አድዋን አደበዘዘው” አሉና አረፉት! (በጉዴ ወጣ! ማለት አሁን ነው!)
በጣም ግርም ያለኝ ምን መሰላችሁ? ህወሐትም ሆነ በአጠቃላይ ኢህአዴግ እስከዛሬ ሲተቹበት የነበረው ዋና ጉዳይ ----- ምስጢረኞች ናቸው፤ ሆዳቸው አይታወቅም እየተባሉ  ነበር፡፡ እናም የህወሐት የቀድሞ ታጋዮች፣ 40ኛ ዓመቱን በማስመልከት ምድረ አርቲስትን ሰብስበው ደደቢት ድረስ ወሰዱ፡፡ ዋና ዋና የትግል ቦታዎችን አስጐበኙ። የትግሉን ገድል ተረኩ፡፡ ከ20 ዓመት በላይ ከርችመውት የቆዩትን ገበና ወለል አድርገው ከፈቱ። (ልብን ከፍቶ እንደ መስጠት እኮ ነው!) እና ይሄ  ጥፋቱ ምንድነው? (የምርጫ ቅስቀሳ ያስብላል!?)
ዝም ብዬ ሳስበው ግን በህወሐት ላይ ለተሰነዘረው ትችት ተጠያቂዎቹ አንዳንድ ስሜታዊ አርቲስቶች ይመስሉኛል፡፡ ደደቢትን ከጐበኙ በኋላ አንዳንዶቹ በEBC ሲሰጡት የነበረውን አስተያየት ሰምታችኋል? አብዛኞቹ ባዩት ነገር የምር መደነቃቸውን ከገፅታቸውም ከአንደበታቸውም ተገንዝቤአለሁ። ጥቂቶቹ ግን ትወና ቢጤ ሳይሞካክሩ አልቀሩም (ተሰጥኦ ለመቼ ነው!) ግን እኮ  ገና መጀመሪያውኑ ተነግሯቸው ነበር፡፡ “ለጉብኝቱ የመጣችሁት እንድትዘምሩልን አይደለም፤ ሁሉም ሰው ያሻውን ሃሳብ ሊይዝ ይችላል” በሚል፡፡ አንዳንድ አርቲስቶች ግን ማሳሰቢያው የገባቸው አልመሰለኝም  (ቀላል ዘመሩ እንዴ!)
በነገራችን ላይ ከበረሃ ትግል ሳይሆን ከዩኒቨርሲቲ ግቢ ወደ ቤተመንግስት ግቢ የመግባት ዕድል ያገኙት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በዚህ የህወሐት 40ኛ ዓመት በዓል ላይ “የታጋይነት ማዕረግ” ተሰጥቷቸዋል፡፡ (“ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” አሉ!) ማዕረጉ የክብር ይሁን የምር ግን አልተነገረንም፡፡ የምር ከሆነ እኮ “ታጋይ ኃይለማርያም” ይባሉበታል ማለት ነው፡፡ የክብር ከሆነ ግን  “የክብር ታጋይ” ነው  የሚባሉት (የክብር  ዶክትሬት እንደማለት!)
አያችሁ---የክብር ዶክትሬት የሚሰጠው ዩኒቨርስቲ ተገብቶ----ትምህርት ተከታትሎ…ጥናትና ምርምር ሰርቶ -- አይደለም፡፡ በተሰማሩበት ሙያ ለአገር ያበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ ተመዝኖ ብቻ ነው የሚሰጠው፡፡ ይሄም ተመሳሳይ ይመስለኛል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ታጋይ የተባሉት ለ17 ዓመት ጠብመንጃ አንግተው ስለታገሉ አይደለም፡፡ (እሳቸው ከብዕርና ከጠመኔ ውጭ ምንም አያውቁም!) እዚህ ጋ መረሳት የሌለበት ቁምነገር ምን መሰላችሁ? እርግጥ ነው አቶ ኃይለማርያም ከትግል ጋር አይተዋወቁም። እርግጥ ነው ጥይት አልተኮሱም፤ እርግጥ ነው ፈንጂም አላፈነዱም፡፡ ግን የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን (መሬት ይቅለላቸውና!) ተክተው ሌጋሲያቸውን ለማስቀጠል ቃል የገቡት፣ ኃላፊነት የተሰጣቸውም ለእሳቸው ነው፡፡ (ታጋይ መባል አይበዛባቸውም!)
ለነገሩ በኢህአዴግኛ፤ ሥልጣንና ሹመትም እንደ ትግል ወይም መስዋእትነት ነው የሚቆጠረው፡፡ አቶ ኃይለማርያም፤ በጠ/ሚኒስትርነት የተሾሙ ሰሞን አዲሱን ስልጣናቸውን እንደ ትግል እንደሚያዩት መናገራቸው ትዝ ይለኛል፡፡ (አገር መምራትን እንደ ትግል ማሰብ አይገርምም?) ኢህአዴግ እኮ ልማት ማካሄዱንም፣ መልካም አስተዳደር ማስፈኑንም፣ የህግ የበላይነትን ማስጠበቁንም፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማጐልበቱንም፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ማስከበሩንም…ወዘተ (ከሀ-ፐ በሉት) እንደ ትግል ነው የሚቆጥረው፡፡ (የትጥቅ ትግል አልወጣኝም!)
አንዳንዴ ሳስበው ግን እውነቱን ነው እላለሁ፡፡ ከምሬ ነው…እነዚህ የተጠቀሱትን ጨምሮ…ኪራይ ሰብሳቢዎችን መጋፈጥ… ድህነትን ታሪክ ማድረግ… ፍትሃዊ የሃብት ሥርጭትን ማስፈን…(ሁሉንም እኩል ማደህየት እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን!) የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ማጠናከር (“ማን ነበር አክትሞለታል” ያለው?!) ወዘተ… ቀላል ትግል እኮ አይደለም፡፡ እንዴ…ደርግን የሚያህል ግዙፍ ኃይል በትጥቅ ትግል ለመጣል እኮ 17 ዓመት ብቻ ነው የፈጀው (ትንሽ ናት አልወጣኝም!) ቀደም ብዬ ያነሳኋቸው የአገር ችግሮች ግን ይኸው ከ20 ዓመት በኋላም “መች ተነካና!” እያስባሉ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ካያችሁት .. የኢህአዴግ ሥልጣን እውነትም መስዋዕትነት የሚከፈልበት ትግል ነው ሊባል ይችላል፡፡ (ተቃዋሚዎች አልገባቸውም!)
ከህወሐት 40ኛ ዓመት በዓል ጋር በተያያዘ የጀመርኩትን ወግ ሳልቋጭ ነው ወደ ትግል ትንተና የገባሁት፡፡ እናም የቀረችኝን ልጨርስላችሁ። አሁንም ጉዳዩ አርቲስቶችን ይመለከታል፡፡ (የህወሐትና የአርቲስቶችን ፍቅር ያዝልቅላቸው!?)
በነገራችሁ ላይ ይኸኛውንም በEBC መስኮት ነው የታደምኩት (ከአንዴም ሦስቴ!) ምን መሰላችሁ? የህወሐትን 40ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ ለአርቲስቶች የተዘጋጀ የጥያቄና መልስ ውድድር ነው፡፡ ቦታው አዳማ ይመስለኛል፡፡ ወይም እርግጠኛ ለመሆን በEBC መስኮት!!
የጥያቄና መልስ ውድድሩ “11በ11” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ለምን? አንደኛ፤ ህወኃት የተመሰረተበት ቀን የካቲት 11 ነው፡፡ ሁለተኛ፤ ጠያቂውን ጨምሮ በውድድሩ የተካፈሉት አርቲስቶች 11 ነበሩ፡፡ እናም 11 በ11 ተባለ፡፡ ምክንያቱ አላጠገባችሁም? (ደግሞ ለምክንያት!) የአሸናፊው ቡድን 5 አርቲስቶች በነፍስ ወከፍ 11ሺ ብር ነው የተሸለሙት፡፡ (የፓርቲ “ሞጃ” ይመቸኛል!) በእነዚህ ሁሉ በቂ ምክንያቶች የጥያቄና መልስ ውድድሩ “11 በ 11” ተብሏል፤ አለ - ውድድሩን የመራው አርቲስት ሸዋፈራሁ፡፡
ጥያቄና መልሱ ተጀመረ፡፡ በነገራችሁ ላይ ጥያቄዎቹ በህወኃት ትግል ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ (በትንሹ የ30 ዓመት ታሪክ ማለት ነው) እኔ የምለው… የእነ ህወሐት ገድል በታሪክ ትምህርት ውስጥ ተካተተ እንዴ? (እነ ፍልፍሉ እሳት ሲሆኑብኝ እኮ ነው!) ይታያችሁ… የታጋዮች የበረሃ ስም… ህወሐት ደርግን ድባቅ የመታባቸው ዘመቻዎች፤ ቦታዎች፣ ዓመተ ምህረቶች ወዘተ ሲጠየቁ ነበር፡፡ መጠየቃቸው አይደለም የሚገርመው።
መመለሳቸው ነው፡፡ ያውም እኮ ከአፍ እየነጠቁ ነበር የሚመልሱት፡፡ ቆይ… የአዲስ አበባ አርቲስትና ኮሜዲያን የህወሐትን ትግል እንዲህ የሸመደዱት መቼ ነው? ይሄውላችሁ… በመልሳቸው ፍጥነት የተገረምኩት እኔ ብቻ ብሆን ኖሮ ችግሩ ከእኔ ነው ብዬ ግለ-ሂስ አወርድ ነበር፡፡ ግን እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡
ራሱ የፕሮግራሙ አጋፋሪ፤ አርቲስቶቹ መልሱን እንደ እሳት ሲተፉበት ደንግጦ “አብራችሁ ታግላችኋል እንዴ?” አይል መሰላችሁ፡፡ (ደንግጦ አስደነገጠን!) እኔማ አውጥቼ አውርጄ ተውኩት እንጂ “ጥያቄና መልሱ …ተጭበርብሯል” ብዬ ለህወሐት ልጠቁም ዳድቶኝ ነበር (“ሃብታም በሰጠ …” እንዳልባል ፈርቼ ጭጭ አልኩ!)
ይልቅስ ምኑ ደስ አለኝ መሰላችሁ? ያሸነፈም የተሸነፈም መሸለሙ!! አሸናፊዎቹ (ቅሬታዬ እንዳለ ነው!) እያንዳንዳቸው 11ሺ ብር፤ በጠቅላላ 55ሺ ብር ሲሸለሙ፣ ተሸፊናዎቹ በነፍስ ወከፍ 5ሺ ብር፣ በድምሩ 25ሺ ብር አግኝተዋል፡፡ እኔ የምለው…አርቲስቶቹ ሽልማቱ ጥሟቸው የህወሓት 40ኛ ዓመት ይደገም ቢሉስ? (ምርጫ መሰላቸው?!)
እኛም እንግዲህ ግልጽ ማመልከቻ ለሚመለከተው ወገን አቅርበን ወጋችንን እንቋጭ … የግንቦቱ አገራዊ ምርጫ እንደ ጥያቄና መልስ ውድድሩ እንዲሆን እንፈልጋለን፤ አሸናፊም ተሸናፊም የሚሸለምበት!! ያሸነፈ ደረቱን የማያሳብጥበት፤ የተሸነፈ አንገቱን የማይሰበርበት ምርጫ ያስፈልገናል። (“ታስፈልገኛለህ” አለች ዘፋኟ!)
እንኳን ለአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት በዓል አደረሳችሁ፤ አደረሰን!!

“አዲስ አድማስ ጥሩ ጋዜጣ እንደሆነች አውቃለሁ፡፡ የጋዜጣው ተከታታይ ደንበኛ ነኝ ባልልም አልፎ አልፎ የማንበብ ዕድሉን አግኝቻለሁ፡፡ እናም ብዙ የሚዳስሳቸው ጉዳዮች መኖራቸው ጥሩ ነው፡፡ እንደ አንዳንድ ጋዜጦች በማስታወቂያ ብቻ የተሞላ አይደለም፡፡ ለወደፊቱም ያልሸፈናችሁትን ጉዳይ እየሸፈናችሁ፣ ያልተዳሰሱ ነገሮችን እየዳሰሳችሁ፣ ተፈላጊነታችሁን እንድትጨምሩና እንድታድጉ እመኛለሁ፡፡”

Published in ዜና

ዳንኤል ክብረት
(ፀሐፊና ተመራማሪ)
      “በአገራችን የግል ፕሬስ ታሪክ ለረጅም ጊዜ ሳይቋረጡ ከቆዩ ጋዜጦች መካከል አንዷ አዲስ አድማስ ነች፡፡ ብዙዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች እጣ ፈንታቸው መቋረጥ ሆኖ ተለይተውናል፡፡  በሁሉም እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ አንባቢያን ሊያነቡት የሚችሉት ጋዜጣ ናት ብዬ አስባለሁ፡፡
ጋዜጣዋ በማህበራዊና በመዝናኛ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር ሲሆን ዜናዎቿም በሰዎች ጉዳይ ላይ ትኩረት  ተደርጎ የሚሰራና “የእኔ” የሚል ስሜትን የሚፈጥር ነው፡፡ በጋዜጣው ላይ ቢስተካከሉ የምላቸው ጉዳዮች ቢኖሩ፣ አምዶች በጉልህ ሊለዩ የሚችሉበት ነገር ቢፈጠር፤ አንድ ሰው ማንበብ የሚፈልገውን አምድ የለመደበት ቦታ ላይ ሄዶ ማንበብ የሚችልበት መንገድ ቢመቻች ጥሩ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ጠንከር ጠንከር ያሉ ፅሁፎች ሊያቀርቡ የሚችሉ አምደኞች ቢጨመሩበት የበለጠ ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
እንግዲህ በቀጣይ የሥራ ዘመናችሁ ጋዜጣዋ የበለጠ እያደገች፣ እየታረመች፤ በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ውስጥ ዘልቃ የምትቀጥል ሆና አባቶቻችን፣ እኛም፣ ልጆቻችንም፣ የልጅ ልጆቻችንም የሚያነቧት ሆና እንድትቀጥል ምኞቴ ነው፡፡

Published in ዜና
Monday, 09 March 2015 11:51

“ብርቱካናማው ጥለት”

ከአስር አመታት በፊት...
ከአንድ ጠኔያም አርብ... ከአንድ ችጋራም ሌሊት... ከብዙ ማፏሸክና መራብ በኋላ...
እንዳይነጋ የለም ነጋ!...
ጦማችንን ያደርን ሶስት ጓደኛሞች፣ ከእነ ርሃባችን ከእንቅልፋችን ነቃን፡፡ የተለየ ነገር የለም፡፡ ኮሜዲኖው ላይ ካለው የሰነበተ ደረቅ ዳቦ በቀር፣ በጠባቧ የጓደኛችን ዳኜ ቤት ውስጥ እህል የሚባል ነገር የለም፡፡
አንድ ሁለት ስንል አመሸን፡፡ ሰዓቱ ገፋ፣ ኪሳችን ሳሳ፡፡ ሂሳባችንን ከፍለን ወጣን፡፡ ምሽቱ ገፍቷል፡፡ የቄራ ታክሲዎች ወደማደሪያቸው ከትተዋል፡፡ ኮንትራት ታክሲ ለመያዝ ደግሞ፣ ገንዘብ የለንም፡፡ ስለዚህ እዚያው ቄራ አካባቢ ያለችው የኪራይ ቤቱ ውስጥ እንድናድር ከጓደኛችን ከዳኜ የቀረበልልን ግብዣ የማንቀበልበት ምክንያት የለንም፡፡
የአከራዮቹን አመለ ክፉነት እየተረከልን ወደ ቤቱ አዘገምን፡፡ ድምጻችንን አጥፍተን ገብተን፣ በሰላም እንድንተኛ እያሳሰበን ነበር፡፡ ማሳሰቢያውን አክብረን፣ የተረፈንን ሽንት ከመንገድ ዳር አራግፈን፣ ኮቴያችንን አጥፍተን ወደ ግቢው ገባን፡፡ የጠባቧን ቤቱን በር በጥንቃቄ ከፍቶ አስገባን፡፡
“መብራት ከበራ አከራዮቼ ነቄ ስለሚሉ ነው!...” በሚል ማብራሪያ፣ በሞባይሉ ብርሃን ወደ ፍራሹ ጠቆመን፡፡
“እራት እና መብራት አይንሳህ!” ትለኝ ነበር አያቴ። ምን እያለችኝ እንደሆነ የተገለጸልኝ አሁን ነው፡፡ ዛሬ እራትም መብራትም ነስቶኛል፡፡ ቢሆንም አላማረርኩም። እራት እና መብራት እንጂ፣ ትራስ አልነሳኝም፡፡ ጨለማን ተከናንቤ አስሬ እያፏሸክሁ ፍራሽ ላይ ኩርምት ማለቴን ያየው ዳኜ፣ እንተራሰው ዘንድ የሆነ የስፖንጅ የማይመስል ጠንከር ያለ ነገር አቀበለኝ፡፡
እንዳይነጋ የለም ነጋ!...
ዳኜ ቀድሞን ከእንቅልፉ ነቅቶ ሲቀሰቅሰን፣ የሆነ ቁርስ ቢጤ አዘጋጅቶ እንደሚጠብቀን እርግጠኞች ነበርን፡፡
በሚጨናበሱ አይኖቼ ዙሪያውን አማተርኩ፡፡ የተመሰቃቀለች ጠባብ ክፍል፡፡ የእንቁላል ጥብስ ሽታ የማያውዳት ደረቅ ቤት፡፡ ምላስ የመሰለች ፍራሽ... ዳማ የመሰለ ብርድ ልብስ... የስፖንጅ ያልሆነ ጠንካራ ትራስ!...
ትራሱን አየሁት - ጥቅል ጋዜጣ ነው፡፡ ኮሜዲኖውን አየሁት - ክምር ጋዜጣ ነው፡፡ ጠረጴዛውን አየሁት - ቁልል ጋዜጣ ነው፡፡
ለጊዜው ከጋዜጣው እንቆቅልሽ ይልቅ፣ የርሃብን እንቆቅልሽ መፍታት ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ዳኜ ማታ ሂሳብ ሲከፍል የተወሰነ ገንዘብ እንደተመለሰለት ትዝ ይለኛል፡፡ ያ የተወሰነ ገንዘብ፣ የተወሰነ ዳቦ (የተወሰነ ህይወት) መግዛት ይችላል፡፡
“በማታው መልስ የሆነ ነገር ግዛና እንቀማምሳ!?...” ስል ጠየቅሁት ዳኜን - ሞት ሞት እያገሳሁ፡፡
የዳኜን መልስ፣ የበሩ ድምጽ ቀደመው፡፡
በሩ ዳግም ተንኳኳ፡፡ ዳኜ ፈጠን ብሎ ሄዶ ከፈተው። ቀደም ብሎ ልኮ ነበር ማለት ነው አልኩ በደስታ ተውጬ፡፡ በበሩ ክፍተት ውስጥ፣ በፌስታል የተጠቀለለ ዳቦ እና የታሸገ ወተት ብቅ ሲል ለማየት ጓጉቻለሁ፡፡
ዳኜ ከጠይም እጅ የተጠቀለለ ጋዜጣ ተቀበለ። ዳኜ  ለጠይሙ እጅ የተጠቀለለ ብር ሰጠ (ከማታ የተረፈውን)፡
ጋዜጣውን አየሁት - ከውስጡ የተጠቀለለ ዳቦ የሌለበትን!...
“ምንም የለውም እንዴ?” አልኩት እንደመናደድ እያደረገኝ፡፡
“ሁሉም አለው!...” አለኝ ዳኜ ፈገግ ብሎ፣ የተጠቀለለውን ጋዜጣ እየፈታ፡፡
አይኖቼን ተጠራጥሬ እንደገና አየሁት፡፡ ግንባሩ ላይ ብርቱካናማ ጥለት ያረፈበት ጋዜጣ ከፊት ለፊቴ ተዘረጋ፡፡ ግራ ተጋብቼ ዙሪያዮን ተመለከትኩ፡፡ የጋዜጣ ትራስ፣ የጋዜጣ ጠረጴዛ፣ የጋዜጣ ወንበር... እና ደግሞ... ከጓደኛዬ ፊት ላይ ሲንቀለቀል የሚታይ ʻብርቱካናማʼ የጋዜጣ ፍቅር!...
ዳኜ ገንዘብ አጥቶ እራት ላይበላ ይችላል፡፡ ለቁርስ ቸግሮት ጦሙን ሊያረፍድ ይችላል፡፡ የወር የቤት ኪራይ ይከፍለው አጥቶ፣ ከአከራይ ጥላ ሊሸሽ ይችላል፡፡ ብዙ--ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን፣ ሳምንት ጠብቆ ቤቱ ድረስ ለሚመጣለት ለብርቱካናማው ጋዜጣ ይከፍለው ገንዘብ አያጣም፡፡
ይህ ከሆነ ከአመታት በኋላ...
እኔም የዳኜን ልክፍት ተለከፍኩ፡፡ ብርቱካናማው ጥለት ይናፍቀኝ ጀመር፡፡ ቅዳሜ ሳምንት ጠብቃ ፍንትው የምትል ብርቱካናማ ናፍቆት ሆነችብኝ፡፡
እዚህ ቀለም ውስጥ...
ከብዙዎች ጋር ዋኝቻለሁ፡፡ በብዙዎች የብዕር ጠብታ ውስጤን አረስርሻለሁ፡፡ ከብዙዎች ጋር አውግቻለሁ፡፡ ተገርሜያለሁ፡፡ ተደምሜያለሁ፡፡ ለአመታት “የተጠበለ” የሳምንት ጥዋ ጠጥቻለሁ፡፡ ወር ተራዬ ደርሶኝ፣ “እኔ አለሁ ባለወር ባለሳምንት!...” ብያለሁ፡፡ ከኑሮ ከፍ ዝቅ በተረፈኝ ፋታ፣ ያቅሜን ያህል ደግሻለሁ... አረረም መረረም የመቻሌን ታህል ነፍስ ያፈራውንʼ አቃምሻለሁ፡፡
እዚህ ቀለም ውስጥ...
ብዙ ስሜቶቼን ነክሬ አቅልሚያለሁ፡፡ ከውጭ ሆኜ መናፈቄን ትቼ፣ በለስ ቀንቶኝ ራሴን ከቀለሙ ጋር ለውሻለሁ፡፡ እዚህ ጋዜጣ ገጾች ውስጥ፣ የውስጤን ስሜት አፍስሻለሁ፡፡ እነዚያ ቅዳሜዎች ላይ፣ ብዙ መከፋቶቼን፣ ብዙ መደሰቶቼን፣ ብዙ እየቅል ስሜቶቼን አትሜ አልፌያለሁ፡፡
አስራ አምስተኛዋ አደይ ስትፈካም... የመስቀል ወፍ ከአዲስ አድማስ ስር ዳግም ለአስራ አምስተኛ ጊዜ ክንፎቿን እየጠፈጠፈች ከተፍ ስትልም... እኔ ከዚህ ቀለም ጋር ነኝ!... ብርቱካናማው ጥለት አብሮኝ አለ!...

Published in ባህል