“የሎሚ ሽታ” ፊልም ፕሮዱዩሰር የሆነው ማቭሪክ ፕሮሞሽን፤ ከኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋር በመሆን በኢቴቪ 3 “ማቭሪክ ፊልሞች የኢትዮጵያ” የተሰኘ የአማርኛ ፊልሞች ብቻ የሚታዩበት ፕሮግራም ጀመረ፡፡
“ፊደል አዳኝ” በሚለው ፊልም ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የጀመረው ፕሮግራሙ፤ በየሳምንቱ ቅዳሜ ከ4፡30 እስከ 6፡30 የሚተላለፍ ሲሆን ሰኞ በተመሳሳይ ሰዓት በድጋሚ ይቀርባል፡፡ የማቭሪክ ፕሮሞሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፌቨን ታደሰ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ከዚህ ቀደም የውጭ ሃገር ፊልሞች የሚታዩበትን “ታላቁ ፊልም”ን መነሻ ያደረገው ፕሮግራማቸው፤ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ 10 ያህል የአማርኛ ፊልሞችን ካቀረበ በኋላ ባለሙያዎች በሚሰጡት የግምገማ ውጤት መሰረት አሸናፊው ፊልም ይሸለማል። በፕሮግራሙ የሚቀርቡ ሁሉም ፊልሞች፣ የሲኒማ ቤት የዕይታ ጊዜያቸውን ጨርሰው የወረዱ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሸንቁጥ አየለ የተጻፈው “ህቡዕ ጣት” የተሰኘ ልቦለድ መፅሀፍ ለንባብ በቃ፡፡ ሃሳቡን በማብላላት እና የወቅቱን ሁኔታ ለማገናዘብ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደው መፅሀፉ፤ 206 ገፆች ያሉት ሲሆን በአህጉራዊና አገራዊ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን እንደሆነና በተለይም የኢትዮጵያን ውስጣዊ ልዩነት በዙሪያዋ ያሉ ጠላቶቿ እንደ መሳሪያ በመጠቀም የራሳቸውን አላማ ሊያሳኩ የሚታትሩበትን ሁኔታ ያስቃኛል ተብሏል፡፡ በ45 ብር ለገበያ የቀረበው መፅሀፉ፤ የደራሲው ሁለተኛ ሥራ ሲሆን ከዚህ ቀደም “የተስፋ ክንፍ” የተሰኘ መፅሐፍ እና መቼቱን ባህርዳር ያደረገ “ማዕበል” የተሰኘ ፊልም በመፃፍና በመተወን ለእይታ አብቅቷል፡፡

ሚዩዚክ ሜይ ደይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ባሳተመው “የኮሌጅ ቀን ግጥሞች” መጽሓፍ ላይ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ውይይት ሊያደርግበት መሆኑን አስታወቀ፡፡ ሬድዮ ፋና አካባቢ በሚገኘው ብሔራዊ ቤተ መፃሕፍት የሚካሄደውን የሦሥት ሰዓታት ሥነጽሑፋዊ ውይይት የመኘሻ ሃሳብ በማቅረብ የሚመሩት የሥነጽሑፍ ባለሙያው አቶ ገዛኸኝ ፀጋው ናቸው፡፡

Saturday, 22 March 2014 12:55

አለቀ በቃ

..ተረት ተረት.. አሉ ባለቤቷ ከአምስት ዓመት የማይበልጥ ዕድሜ ያለው የሚመስል አንድ ወንድ ልጅ እየተመለከቱ። ቤቱ ሬሳ የወጣበት ይመስል ጭር ብሎ ነበር፡፡
ከባንኮው በስተውስጥ ቆመዋል፤ ባለቤ.. በስተ ውጭ፤ በጎን በኩል፣ ሁለት የሰፍነግ ትራስ ተደራርቦ እተመቻቸበት ሶፋ ላይ አንድ ረዘም ያለ ቀጭን ሰው እግሮቹን በሰፊው አራዝሞ ተቀምጧል። የራሱ ጸጉር ከግምባሩ መካከል አንስቶ እስከ ማጅራቱ ተረተር ድረስ በቀጭኑ ተመልጧል፡፡ በረጅም መቃ ዓይነት ነገር የተሰራ ሲጃራውን፣ ባውራጣቱና በትንሽ ጣቱ መካከል አሾልኮ ፣ በሌባ ጣቱ ጫን እያለ፣ ካለፍ አገደም ወደ አፉ በመውሰድ፣ የጭስ ኩቦቹን እያከታተለ ቡልቅ ቡልቅ ያደርጋል፡፡ ዓይኖቹ በር በሩን ይመለከታሉ፡፡
“ተረት ተረት” አሉ ባለቤቷ ደግመው “የላም በረት” መለሰች አንዲቷ ቆንጆ፤ አንድዬ በብዙው አንድዬ በትንሹ ሲጃራዋን እየመጠጠች፣ እንደሰውዬው የጭስ ኩቦች ለመሥራት ትደክማለች። አልፎ አልፎ ምትን እያላት እንደሳል ያረጋታል፡፡ በሥራው የሠለጠነው ቀጭኑ ሰውዬ የጎድን አየት እያረጋት ሳቅ ይላል፤ እያከታተለ አንድዬ በዝግታ፣ አንዴ በፍጥነት ኩቦቹን በማስወጣት፡፡
..ተረት ተረት.. አሉ ባለቤቷ ለሦስተኛ ጊዜ
..የላም በረት.. አለች መልሳ፤ ኩቦቹን ለመስራት እየተጋለች፤ ቆንጆዋ፡፡
..አንቺ አልተጠራሽም.. አሉ ባለቤቷ ኮስተር ብለው
ትንሹ ልጅ እክፍሉ ውስጥ ከተኮለኮሉት ሶፋዎች መካከል ረጅሙ ሶፋ ላይ ተቀምጦ ካርታ በመደርደር ይጫወት ነበር፡፡ ቆንጆይቱ ድንገት ብድግ ብላ መጥታ ካርታውን ከልጁ እጅ መንጭቃ ወስዳ የካርታ ጥንቆላ ጀመረች።
..ምነው አስረስ ተረቱን ንገረን እንጂ.. አሉ ባለቤቷ ዋጋ የሚያስከፍል በሚመስል ድምፅ፡፡
“አንድ ቤት ሁለት ውሾች ነበሩ፡፡” ጀመረ አስረስ “ቤቱ ቀዳዳ ነበር” ቀጠለ አስረስ የተነጠቀውን ካርታ እየተመለከተ “በቀዳዳው ወጡ፡፡”
“ታዲያስ” አሉ ባለቤቷ
“አለቀ በቃ” መለሰ አስረስ፡፡ ዓይኖቹ ከካርታው ላይ አልተነቀሉም፡፡
“እሺ ፍቅርስ እንዴት ያረጋል?” ቀጠሉ ባለቤቷ፡፡
“ያስለቅሳል” አለ አስረስ እንባው እንደመጣበት ዓይነት
“ያስለቅሳል? ከየት አመጣኽው ደሞ እንዲህ ያለውን መልስ?” ከባንኮው ወደሶፋው መጥተው ቀና አርገው ዓይኑን ይመለከቱታል፡፡
“ምነው ምን ሆንክ”
“ያስለቅሳል”
“አይ ለቅሶ እዚህ የለም፣ የምን ያስለቅሳል ነው ደሞ” ይቀጥላሉ ባለቤቷ ቆጣ ባለ አንደበት፤ ወዲያው ፊቱን አበስ አበስ በማድረግ “በል እንግዲህ አሁን ንገረኝ፤ ፍቅር ምን ምን ይላል?” በማለት
“ስኳር ስኳርም አይል ........ማር ማርም አይል.......
“ጋብዙኝ” አለች ድንገት እጎኔ ተስጋ፣ ካርታ ቀሚዋ፡፡ ስትጠጋኝ አላየኋትም፡፡
 “ጋብዙኝ” አለችኝ ደግማ
“ቢራ ጠጭ” አልኳት፡፡ “እሺ” አለችና ትንሽ “ጅን” ጠብ ያለበት “ቤርሙጥ” አምጥታ እጎኔ ተመልሳ ተቀመጠች። ባለኩቡ እግሩን አንጠራርቶ ባንኮው ወገብ ላይ ወግቶ በመወጠር ተዝናንቷል።
“ድገሙኝ” አለችኝ፤ ስትጨልጠው አላየኋትም፡፡ ደገመች፡፡ ከሰውዬው ሲጃራ ለምና አመጣችና በመለኮስ ኩቦቹን ለመስራተ ትፍጨረጨር ጀመር እንደገና። ለኔ ለማሳየትም ይሁን ነገሩ አልገባኝም። እኔ ለራሴ የሲጃራ ሽታ ያሰክረኛል፤ አልወድም፡፡ ደጉ ነገር ፈንጠር ብዬ ነበር መስኮት አጠገብ የተቀመጥኩት፡፡ የቀዩ አምፖል ብርሃን ውጋጋን ፊት ላይ በማይንተገትበት በኩል፡፡ የምጠጣውም የጊዮርጊስ ቢራ ነበር፡፡
“ቆንጆ ፎርም አለኝኮ” አለችኝ ቀስ ብላ
“ጥሩ ነው” አልኳት ከጪሱ በመሸሽ.
“ላሳይህ” አለችኝ
“አየሁትኮ” አልኳት
“የለም አላየኽውም” አለችኝ
“አልገባኝም” አልኳት
“ሦስት ዊስኪ ብትገዛልኝ አሳይሃለሁ” አለችኝ፡፡
“ምን? ልብስሽን......” አልኳት ዓይኔ ሳልወድ
ጎርጮ
“አዎ ምናለበት........
“ኧረ ተይ.....”
..ልታይ አይደለም..
..ሁላችንም እያለን?..
“ምንድነው ስድስታችን አይደለንም....” አለች እንደሷ ዓይነት ቆንጆ ጓደኛዋን እየተመለከተች፡፡
“ታዲያ አትፈሪም?”
“ምን ታደርጉኛላችሁ? አትበሉኝ”
“በምን ታውቂያለሽ?”
“አይ ከበላችሁኝም ሕግ አለ”
“አሁን እውነት ካንጀትሽ ነው?”
በቀኝ እግሯ መሬቱን መታ መታ እያደረገች፤ ሐሳቧ ርቆ የሄደ፣ ከንፈሯ ብቻ የሚንቀሳቀስ በሚመስል ሁኔታ፡፡
“አይ ለውስኪው ሰስተህ እንደሁ ተወው.. አለችኝ
“ሰውነትሽን በመጠጣት ለመርሳት ትፈልጊያለሽን?” አልኳት፡፡
“ሳልጠጣ ሰው መሆኔን አውቀዋለሁ መቼ አልኩህ?” ስትል መለሰችልኝ፡፡
“እኔ መቼም ሰው ነሽ እላለሁ” አልኳት
“ሰው ስለሆንኩማ መጠጥ እፈልጋለሁ፡፡”
“የሰው ምልክቱ መጠጥ ነው?”
“አይ ለዊስኪው ሰስተህ እንደሁ ተወው”
“እውን አሁን ያልሽውን ታደርጊያለሽ?”
“ለምን አላደርግም”
“አይ እንዲያው አልመሰለኝም”
መልስ ከመስጠቴ በፊት ብዙ ጊዜ ቆየሁ፡፡
“እንድመልስልህ ከፈለግህ ዊስኪውን ግዛልኝ..
“እንግዲያውስ ጠጪ” አልኳት፡፡ እንዴት እንደሄደች የምታውቀው ራሷ ናት፡፡ አንድ ግማሽ ጠርሙስ ዊስኪና አንድ ብርጭቆ ይዛ መጣች፤ ቀዳች። ባንድ ትንፋሽ ጠጣችው፡፡ ደገመች አሁንም ባንድ ትንፋሽ ጠጣችው፡፡ የነፍስ ስልክም ነፋስ እንደሆነ አላውቅም፤ እውነትም ጠምቷት ኖሯል፡፡
አየት አደረገችኝ፡፡ ..ትዊስት.. የሚባለው የዳንስ ሙዚቃ መሰማት ጀመረ። ከወንበሯ ላይ እያለች እንቅስቃሴዋን ጀመረች፡፡ ሦስተኛ ጊዜ ዊስኪዋን ቀዳች፡፡ ገንዘቤ መሆኑ ተሰማኝ።
“ታዲያስ ተነሻ” አልኳት
የምትንጠራራም መሰለኝ። ሰው የምትጠራም መሰለኝ፡፡ ሽንጭና ዳሌዋን፣ ጣቶቿንና ክንዷን የምታሳየንም መሰለኝ። አንደኛውን ጫማዋን አወለቀች፡፡ ሁለተኛውን ደገመች። ከወገቧ ጎብደድ፡ ከሽንጥና ከዳሌዋ ጎበጥ፣ ከደረትና ከትከሻዋ ቀና ብላ ግራ እጇን አራዝማ፣ በቀኝ እጇ ከግራ ከእጇ መዳፍ ጀምራ፣ ክንዷን ፣ ጡቶቿን እስከ ቀኝ ትከሻዋ ጫፍ ድረስ በቀስታ እየደባበሰች ታሪካዊ አነካሥ አሳየች። ወደፊቷም እንደመንደርደር ብላ አንገቷን ብቻ ዘወር በማድረግ አንድ ባንድ አየችን፡፡ ቀስ እያለችም ወደ እኔ ዞረች፡፡ እጇንም በማሽቆልቆል ከቁርጭምጭሚቷ ጀምራ ባትና ጭኗን እየደባበሰች ወደ ደረቷ አመጣችው፡፡ እግረ መንገዱንም ሰውነቷን ገለጠው። የባት ጡንቻ የላትም፣ ሙላው ሙሉ ነው፡፡ እንደገና አየት አደረገችን፤ ሳቅ አይሉት ሳቅ ሳቀች፤ አስፈራችኝ። ወዲያውም “ልድገም ወይ” አለችኝ ፤ ዓይን ዓይኔን እየተመለከተች፡፡ ባለኩቡ ቀድሞ ድገሚ አላት፡፡ የሚሠራው የጭስ ኩብ ራሱ ላይ ይትጎለጎላል፡፡ እኔ ነገሩም አልገባኝ፣ እሷና እሱ ግን ተግባብተዋል። የምትደግመው፣ ያሳየችውን ትርኢት ሳይሆን ውስኪውን ኖሯል፡፡ አራተኛው ብርጭቆ ስሙ እውነትም ድጋሞሽ ከሆነ ደገመች፤ ትርኢቱ ቀጠለ፡፡
ሶፋ ላይ ነበር የተቀመጥኩት፤ እግሮቼን አዝናንቼ፤ መጣች፡፡ በኋላዋ ወደ እኔ፡፡ እጭኔ ውስጥ ቀስ እያለች ገብታ ቆመች፡፡ ጭንና ጭኔን እየነካካች። ቀስ እያለችም ፊቷን ወደኔ አዞረች፡፡ እኔ አዟዟሯን ስመለከት ዱሮ ሹራቧን አውልቃለች፡፡ የት እንደወረወረችው ግን እግዜር ይወቅ፡፡
ከላይ የለበሰችው ስስ ሸሚዝ ነው። ጉርድ ቀሚሷ በሰፊ ቀበቶ ታስሯል። ደረቷን ሰፋ አድርጋ ቆማ ቁልቁል ተመለከተችኝ፡፡ ከመቅጽበትም በረጃጅም ጣቶቿ፣ ጸጉሬንና አንገቴን ስትዳብሰኝና ቀሚሷ እጫማዬ ላይ ሲወድቅ አንድ ሆነ፡፡ ዓይኔ አብሮ ወደ ሆዴ ገባ፡፡ ቱር ብላ ወደ ወለሉ ስትወጣ እንኳ የሚታየኝ እንደህልም ነበር፡፡ ብንን ያልኩት ብቻ እሜዳ ላይ ሳያት ነው፡፡
ተመስገን ነው! ሆኖም ታዲያ የውስጥ ልብሷን አላወለቀችም፤ ብዙም ሳይቆይ ወደ እኔ ቀስ እያለች ተጠጋች፡፡ እንደ በፊቱ ግን አልተሞኘሁም፤ እግሬን ሰብስቤያለሁ። ምን ያረጋል? እሶፋው ገሌንችና እገራ ጭኔ ላይ ጀርባዋን ሰጥታ ተቀመጠችብኝ። የተወለወለ ነው ጀርባዋ። ጠባሳና ዥንጉርጉርነት አይታይባትም፡፡
“ቁልፉን ከኋላዬ ፍታልኝ” አለችኝ
“የምኑን” አልኳት
“የጡት መያዣዬን”
..እንዴት ነው?..
..አይዞህ ንጹህ ነኝ፤ ምን አስፈራህ? ጡቴን ማየት ጠላህ እንዴ? የወደቀ መስሎህ እንደሁ.. አለችኝ፡፡
..የለም ለሱ እንኳን.....” ብዬ በመመለስ፣ ራሴን ማደፋፈሪያ ነገር ልናገር ስጀምር እንደትሬንታ የሚጮህ፣ የካርታ ድርጅት ታርጋ ያለበት “ቼብሮሌት” ኦቶሞቢል ወደ ነበርንበት ገደማ መጣ። ቆመ፡፡
“ታዲያ ምንድንው ፍታልኛ” አለችኝ። ልፈታ ስፈራ ስቸር ሁለት ፈረንጆችና አንድ ኢትዮጵያዊ እኛ ወዳለንበት ገቡ፡፡ ዱሮ በምታውቅበት ዘዴ ጡቷን ነቅነቅ፤ ደረቷን ሰበቅ ስታደርግ ጡት መያዣዋ ጧ ብሎ ኖሯል፡፡ ውጥርጥር ያለ ጃኬት የለበሰው አንደኛው ፈረንጅ፤ ፊቱ ድንገት ደም ለብሶ ተንደርድሮ መጥቶ ታቅፎ ሲያሽከረክራት ሁኔታው ታየኝ፡፡
የቤቱ ውስጥ ባንዳፍታ ነፍስ ዘራ፡፡ አንዲቷ ዙሪያ ጠረጴዛ መጥረግ፣ አንዲቷ መቀመጫ ማስተካከል፣ አንዲቷ ክንድ መጥለፍ ጀመሩ፡፡ ልጅቷን ጥርቅም አርጎ አቅፏት የነበረው ፈረንጅ ድንገት ለቀቃት፡፡
በቅጽበትም አንድ ስቴካ “ዊንስተን” ሲጃራ ከጃኬቱ ውስጥ አውጥቶ ከፈተና እቤቱ ውስጥ ላለው ሁሉ ማደል ጀመረ፡፡ እየወረወረ። ያመለጠ ንም ብንኖር ከመሬት አንስተንም ቢሆን ሲጃራችንን እየኪሳችን አደረግን፡፡ እኔ እንኳን አላጨስም ነበር፤ ከማን አንሼ፤ አልተግደረደርኩም፡፡
ኩብ ሠሪው ኢትዮጵያዊ የዱሮ ባኮውን ቀደደና ሲጃራውን ተያያዘው፡፡ የሱም ተማሪ ቀደደችና ተያያዘችው፡፡ “እስቴካው” ሲጃራ አላለቀ ኖሮ ድጋሚ ሊሰጠን ሲል፣ ባለቤቷ ከባንኮው ወጥተው ነጠቁት፡፡ “ሌላ ባለ ሱስ ሞልቷል” ብለው። የተረፈውን በሙሉ አውጥቶ ጨመረላቸው፡፡ ኢትዮጵያዊውና አንደኛው ፈረንጅ ተመቻችተው ተቀመጡና መሎቲ ቢራ ተቀዳላቸው፡፡ ጋባዣችንም ፈረንጁ ትንሽ ወዲያ ወዲህ ካለ በኋላ ተቀመጠ፡፡ ግብዣዬን የተቀበለችው ወይዘሮ እግዜር ይስጥልኝ እንኳ ሳትል ዱሮ ሄዳ እሱው ላይ ተጠመጠመች፡፡ እጎኔ የነበረውን ወንበር ወደሪቴ አሽቀንጥሬ እግሬን እላው ላይ ዘረጋሁት። ዘርግቼ የማላውቀው ሰውዬ። ቢራዬንም ጭልጥ አደረግሁና፣ “ውስኪ ብላክ ኤንድ ሁዋይት” አልኩኝ ድምጼን ከፍ አድርጌ፡፡ ውስኪው ተቀዳልኝ፤ ባንድ ትንፋሽ ጭው አረግሁት፡፡ “ድገሚኝ” አልኳት። ስትደግመኝ ሁለተኛው ቅጂ ተቀጣጥሎ ቁርቢል “ድቡል” አልኳት፤ ሳቅ ብላ “ድቡል” ቀዳችልኝ፡፡
“አስረስ” አሉ እመይቴ “ተረት ተረት”
“ባንድ ቤት ሁለት ውሾች ነበሩ፡፡ ቤቷ ቀዳዳ ነበር፡፡ በቀዳዳው ወጡ፡፡”
“ታዲያስ”
“አለቀ በቃ፡፡”
“ጋብዘኝ” ትላለች የኔ ተጋባዥ፤ ታቅፏት የነበረውን ፈረንጅ እያሻሸች፡፡ ሲጃራዬን ከኪሴ መዠረጥሁት “ክብረቲት እባክሽ” አልኳት፡፡
እውጭ ስወጣ፣ አጥሩ ሥር እነበረው ቁሻሻ ውሃ መውረጃ ውስጥ ልገባ ነበር፡፡ ቀና አልኩኝ፤ አለፍ አለፍ እያለ የደመና ኩብ ይትጎለጎላል፡፡ የቤቴን መንገድ ስያያዝ ማካፋት ጀመረ፡፡

Published in ልብ-ወለድ

የመጽሐፉ ርዕስ -  የንጉሡ ገመና
የገጽ ብዛት - የ172
የታተመበት ዘመን - 2006 ዓ.ም
የሽፋን ዋጋ - ብር 49.75
አሳታሚ - ግርማ ለማ
የመጽሐፉ ይዘት ከታሪክ ዘውግ የሚመደብ ሆኖ አሳታሚው ሁለት ምንጮችን ተጠቅመው ነው ያሳተሙት፤ እነሱም ለ14 ዓመታት በንጉሥ አሽከርነት ያገለገሉት የአቶ ሥዩም ጣሰው መንዜው የግል ማስታወሻና የልዩ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽ/ቤት ቀይ ሽብርን አስመልክቶ ያሳተመው “ደም ያዘለ ዶሴ” የተሰኙ መፃሕፍት ናቸው፡፡
በተለይ አቶ ሥዩም ከልጅነታቸው ጀምረው በቤተመንግሥት ያደጉና ለድፍን 14 ዓመታት በንጉሡ አሽከርነትና አልባሽነት ያገለገሉ በመሆናቸው የንጉሠ ነገሥቱን ጓዳ ጐድጓዳ፤ የአሽከሮችን፣ የደንገጡሮችንና የወቅቱን ባለሥልጣናት ጠቅላላ ሁኔታ የማየት ብቻ ሳይሆን የማወቅ ዕድሉ ስለነበራቸው ማስታወሻቸው ተአማኒነት ይኖረዋል። አቶ ሥዩም ንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣናቸውን ተቀምተው መጀመሪያ በቤተመንግሥታቸው ቀጥሎም በ4ኛ ክፍለ ጦር እስረኛ እስከሆኑበት ድረስ ንጉሡን በታማኝነት አገልግለዋል፤ በደርግ ዘመን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ኖረው ኢህአዴግ ሲገባ በቁጥጥር ስር መዋላቸውና ከጠባቂዎች አምልጠው ራሳቸውን ማጥፋታቸው ይነገራል፡፡ ወደ መጽሐፉ እንመለስ፡፡
አሳታሚው ግርማ ለማ፤ በምስጋና ገጹ ላይ የጽሑፉን ዋና ቅጅ (ኦሪጅናል) የሰጠው “በያን ናስር” የተባለ ሰው መሆኑን ጠቅሷል፤ ግን በያን የሥዩምን ጽሑፍ እንዴት እንዳገኘው ወይም የሥዩም ወኪል ይሁን፤ የገለጠልን ነገር የለም፤ የተገኘበት መንገድ ቢጠቀስ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሥዩም የሞተው በድንገት ነው፤ የተያዘውም ሳያስበው ቤቱ በታጣቂዎች ተከቦ ነው፡፡ ስለዚህ ሃሳባችንን ወደአልተፈለገ ጥርጣሬ እንዳያመራን ግርማ ረቂቁን እንዴት እንዳገኘው ቢገልጥልን መልካም ነበር፡፡ የተጻፈልን ታሪክ ነዋ! ታሪክ ያለአስተማማኝ ማስረጃ ሊታሰብም ሊጻፍም እጅግ ይከብዳል፡፡
መጽሐፉ የምስጋናና የመግቢያ ገጾችን ሳይጨምር፣ በዘጠኝ ምዕራፎች የተዋቀረ ነው፡፡ ስምንቱ ከስዩም ጣሰው ማስታወሻ የተወሰዱ ሲሆን ዘጠነኛው ምዕራፍ “ደም ያዘለ ዶሴ” ከተባለው መጽሐፍ የተገለበጠ ነው፡፡
የመጽሐፉ ጠንካራ ጐኖች
መጽሐፉ በንጉሡ ጓዳና ቢሮ ውስጥ ስለነበረው እውነት የገለጠልን በመሆኑ፣ የንጉሠ ነገሥቱን አጠቃላይ ሰብዕና ለሚያጠና ሰው ትልቅ የታሪክ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ንጉሡ በካህናትና ባለሥልጣናት ዘንድ ተፈርተው ይከበሩ ስለነበር፣ ድምሩ ህዝብም አባቱን እየተወ “ኃይለሥላሴ ይሙት” በማለት በስማቸው ይምልና ይገዘት ነበር፡፡ ግን እንደ ሥዩም ጣሰው ጓዳቸውን ገብቶ የማየት ዕድል ቢገጥመው ኖሮ ምን ያህል ሲታለል እንደኖረ ይገባውና ከልቡ ይቆጭ ነበር ያሰኛል፡፡ ለማንኛውም የመጽሐፉን ጠንካራ ጐኖች በአምስት ከፍያቸዋለሁ፡፡
ገመና አንድ
ንጉሡ ተደባዳቢ ነበሩ
ንጉሡ አሽከሮቻቸውን ይደበድቡ ነበር፤ “…የፀጉር ቅባት ፓንተን ሳቀርብላቸው ቀና አሉ፤ አዩኝ፡፡ አሰቡ አሰቡና ‘ማታ ማነው ፍራፍሬውን የደገሰው’ ብለው ጠየቁኝ፡፡ እኔም ራሴ መሆኔን ነገርኋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ብድግ አሉና ተያያዙኝ፡፡ እስከሚደክማቸው ድረስ ደበደቡኝና ቁጭ ብለው ፀጉራቸውን አበጠሩ፡፡ ክራባታቸውን አሰሩና ተነሱ። ልብሳቸውን ለብሰው ሲጨርሱ ጠሩኝ፡፡ እኔም አቀርቅሬ ተጠጋሁ፡፡ አስጐነበሱና እስከሚበቃቸው ወገሩኝና እየተሳደቡ ወደ ቁርሳቸው ሄዱ” (ገፅ 11-12)
ይህን አይነት እርግጫና ጥፊ ለሥዩም አዲስ አልነበረም፤ በየጊዜው ይገረፋል፤ የስድብ ውርጅብኝ ይዘንብበታል፡፡ ሁለት ቀን ብቻ ከተገረፈ በኋላ ብር እንዲሰጠው አድርገዋል፤ ይህ አንድም ምሥጢራቸው እንዳይወጣ ማባባያ ነው፡፡ አለዚያም ካሣ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሆኖም የሥዩም (አሽከርና የታሪኩ ፀሐፊ መሆኑን አንዘንጋ) ትልቁ ፈተና ከንጉሡ ዱላ ይልቅ የሴት አሽከሮች በእሱ ላይ ማደምና ከባለሥልጣናት ጥርስ ውስጥ ማስገባት ነበር ትልቁ ፈተና የሆነው። ለዚያ ሁሉ እርግጫ፣ ጥፊና ዱላ ሰበቡ ንጉሡ የገረዶችንና የአሽከሮችን ወሬ ስለሚሰሙ ነው፡፡ (ገፅ 14)
ንጉሡ ወሬ ይወዳሉ፤ የሆነ ያልሆነን ሁሉ የሚቀላምድላቸውን ሰው ያስጠሩትና ምንም ሳያጣሩ የተወራበትን ሰው ራሳቸው ይገርፋሉ፤ ካስፈለገም ግዞት ይልካሉ፡፡ (ገፅ 21 እና 24)
ገመና ሁለት
ንጉሡ ሴሰኛ ነበሩ
ንጉሡ ሴት በጣም አብዝተው ይወዱ ነበር፤ በዚህ የተነሳ ከጽዳት ሠራተኞች፤ ከአበሻ ወጥ ቤቶች፣ ከእንጀራ ጋጋሪዎች፣ ከቅንጬ ቤቶች፣ ከሴተኛ አዳሪዎች፣ ከሆስተስና ከባለ ትዳር ሴቶች ጋር ይቀብጡ ነበር፡፡ “ሴቶቹ አብዛኛውን ጊዜ የሚገቡት ቀን ከምሳ መልስ እረፍት በሚያደርጉበት ጊዜ ከ8-10፡30 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ጃንሆይ ገብተው ከተኙ በኋላ ትንሽ ቆይተው ደወል ይደውላሉ፡፡ በዚያ ጊዜ በዚህ ነገር የተለየ ባለሟል የሆኑ አሽከሮች በተራቸው ይገቡና “ዕገሊትን ጥራ” ሲባል ይጠራል፡፡ ምን አልባት እርሱ ከተጠራችው ሴት ጋር ሽርክና ከሌለው ወይም ከምትወስደው ገንዘብ በብዛት ካላካፈለችው “እርሷ አሁን የለችም” በማለት የርሱ ሽርክ በየጊዜው ብዙ ገንዘብ የምትሰጠውን ሴት “ዕገሊት አለች፤ እርሷ ከሥራዋ ላይ አትጠፋም” በማለት ይቀላምድና ይጠራል፡፡ ሲገቡና ሲወጡ የተለየ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ሴቶቹ በሚያሳዩት መለዋወጥ የተቀረው ሰው እዚያ ቦታ እንደደረሰች ይገባዋል” (ገፅ 51)
“ቢሮ የሚደረገው ደሞ ሌላ ነው፤ ቢሮ በሚሠሩበት ጊዜ ረፈድ ሲልና አንዳንድ ባለሥልጣኖችን ካነጋገሩ በኋላ ገለል ብለው ቢሮ አጠገብ ካለው መኝታ ቤት ጐራ ይላሉ፡፡ ከዚያም በዚያ አካባቢ ከሚሠሩት ሴቶች ውስጥ የፈለጓትን አስጠርተው ትንሽ ከተጨዋወቱ በኋላ ወደ ቢሮአቸው ይገባሉ፡፡ …ሆስቴሶችንና ሌሎችን ደግሞ እምድር ቤት ካለው ቢሮ ነው የሚያገኙአቸው”    (ገፅ 51)
ይህ ሁሉ ሲሆን እንደየሴቶቹ የንቃት መጠን ዛቅ ያለ ገንዘብ ይከፈላቸዋል፤ ከሥራ ቤት፣ እንጀራ ቤትና ወጥ ቤት ለሚመጡት ሴቶች የሚከፈላቸው አነስተኛ ገንዘብ ሲሆን ለጽዳት ሠራተኞችና ለሌሎች ሴቶች ግን ከ70-80 ሺህ ብር ይከፍሉ ነበር፡፡ ሴቶቹ ደግሞ ወደ ንጉሡ ላቀረባቸው ሰው (ደላላው) ከ5-10 ሺህ ብር ቀረጥ የመክፈል ግዴታ ነበረባቸው። በዚህ የተነሳ ከንጉሡ ጋር የተገናኙ ሴቶች ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቆንጆ ቪላና ዘመናዊ መኪና ይገዙ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ እንዲያውም ፖለቲካዊ ሥልጣኑን ተቆጣጥረው የፈለጉትን ያስሾሙ ያስሸልሙ፤ የጠሉትን ደግሞ ያሰቃዩት ነበር (ገፅ 51)
አንዳንድ የንጉሡ ውሽሞች በጣም ቀበጦች ስለነበሩ በመንግሥት ወጭ፣ አስተርጓሚ ጭምር ተመድቦላቸው ለሽርሽር ፈረንጅ አገር ይሄዱ ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ግን ንጉሡ የባለቤታቸውን የዕቴጌ መነን አስፋውን ጌጣጌጥ ሳይቀር ለውሽሞቻቸው መስጠታቸው ነው፡፡ ለአንዳንድ ውሽሞቻቸውም ቋሚ ደሞዝ ተቆርጦላቸው የቤተ መንግሥት አሽከሮች በየወሩ እቤታቸው ድረስ እየሄዱ ይከፍሉ ነበር፡፡ (ገፅ 56)
ይህ ድርጊት ያንገበገበው ሥዩም “ኢትዮጵያ በተለይ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ስትገዛ የኖረችው በንጉሠ ነገሥቱ ሳይሆን በእልፍኝ አስከልካዮች፣ በጥቂት የእልፍኝ አሽከሮችና በገረዶች ነበር፡፡ …ቤተመንግሥቱ ቤተመንግሥት መሆኑ ቀርቶ ፍጹም የሰይጣን ቤት ሆኖ ነበረ” ሲል ትዝብቱን አስፍሯል። (ገፅ 20)
ገመና ሶስት
ንጉሡ አይጾሙም ነበር
ንጉሡ አክሱም ጽዮንንና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን ስለአሠሩ ካህናት ያወድሷቸዋል፤ ይሰግዱላቸዋል፡፡ “አቤቱ ፍርድን ለንጉሣችን ስጠው” እያሉም ዘወትር ይፀልያሉ፤ እንደ ጻድቃንና ሰማዕታት በመቁጠርም መልክአ ኃይለሥላሴ ደርሰውላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ንጉሡ የክርስቲያንን ህግና ሥርዓት በመጣስ፣ አርብና ረቡዕን እንዲሁም ሌሎች አጽዋማትን አይጾሙም ነበር፡፡ (ገጽ 25 እና 34)
ገመና አራት
ንጉሡ ጠንካራ ሰራተኞችንና ታማኞችን አይወዱም ነበር
“ግርማዊነታቸው የሚወዱት ሰው ፈጣን፣ አጭበርባሪ፣ አሳባቂ፣ በዕውቀት ያልበሰለ፣ እርሳቸውን አምታቶ የሚያታልላቸውን ሰው በጣም ይወዱታል፡፡ የጥቅም ተካፋዮቻቸው በሙሉ በዕውቀት ያልበሰሉ፣ የሰውን መብት በፍጹም ያልተረዱ፣ ሰውን ሸጠው ለመክበር ብቻ ጽኑዕ ዓላማ ያላቸው፣ ለኔ እንጂ ለኛ የሚል መንፈስ ፈጽሞ የሌላቸው ጨካኞች፣ ሰው በችግር ሲሰቃይ ሲያዩ ከማዘን ይልቅ መደሰትን የሚመርጡ ከንቱዎች ናቸው፡፡
“ግርማዊነታቸው አጥብቀው የሚጠሉት ሰው እውነትን በጣም አድርጐ የሚወድ፣ ዘወትር የሚከራከራቸው፣ በእውነት ፍጹም በሆነ መንገድ የሚወዳቸው፣ ሲዋሹ የሚያስተባብላቸው፣ የሚታሙበትን ነገር እንዲተው የሚነግራቸው፣ የማይንቀዠቀዥ፣ አዋቂ ሰው በፍጹም አይወዱም” (ገፅ 31) ይለናል፤ ሥዩም በ14 ዓመት የአሽከርነት ዘመኑ የታዘበውን ሲያካፍለን፡፡
ገመና አምስት
ንጉሡ ስስታም ነበሩ
ንጉሠ ነገሥቱ ኢትዮጵያን የምታክል ታላቅ አገርና እጅግ ብዙ ህዝብ የመግዛታቸውን ያህል ስስታቸውም ያን ያህል አሳፋሪ እንደነበር በመጽሐፉ ላይ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፡፡ በልጅነት ዘመናችን የምናውቃቸው ንጉሥ፤ በየቦታው ሲዘዋወሩ ብር እንደጥሬ እየበተኑ የሚሄዱ መሆናቸውን ነበር፡፡
ሥዩም የሚያውቀውን እውነት ሲነግረን ግን ስስታቸው በጣም የወረደና ለማመን የሚያስቸግር ሆኖ እናገኘዋለን “…በተለይ ከኬኩ ትንሽ በቄንጠኛ አኳኋን ቆርሰው ከበሉ በኋላ በምልክት አድርገው በጥንቃቄ እንዲቀመጥ ይናገራሉ፡፡ በማግስቱ ሲመጣ ትንሽ ለውጥ ከታየበት “ማነው የተጫወተበት” በማለት ማሰቃየት ነው፡፡ አንድ ኬክ ከሶስት እስከ አምስት ቀን ድረስ እየተመላለሰ ይቀርባል፡፡ ለምሳሌ ሐሙስ ቀን ተጀምሮ እንደሆነና ቅዳሜ ደብረዘይት ቢሄዱ አብሮ ይሄዳል፤ ማሩንም በጣም አድርገው ይቆጣጠራሉ፡፡ ከማስቀመጫው ብልቃጥ ውስጥ ትንሽ ጐድሎ ያገኙት እንደሆነ “እንደፈለጋችሁ ትጫወቱበታላችሁ” ብለው መለብለብ ነው” (ገፅ 33) ሲል ያየውን ትዝብት ያካፍለናል፡፡
ከዚህ ሌላ መኝታ ቤታቸው በስጦታ ዕቃዎች፣ በቸኮላት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ስለሚሞላ ዕቃ ቤት ይመስል ነበር፤ እንዲያውም አትክልትና ፍራፍሬው፤ እንዲሁም ቸኮላትና ኬኩ እየተበላሸ የመኝታ ቤታቸውን ሽታ ያበላሸው ነበር፡፡ (47፣ 116፣ 117)
ከመጽሐፉ ውስጥ በጣም የገረመኝ ቢኖር (ገፅ 149) ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ ለንጉሡ ልክ “ልዩ ካቢኔ” ይባል እንደነበረው የስለላ ተቋም፣ በየቀኑ ለንጉሡ ደብዳቤ ይልኩ የነበሩ መሆናቸው ነው፤ ለመሆኑ ቀኛዝማች ተሥፋን ከንጉሡ ጋር ያውም በየቀኑ የሚያገናኛቸው ምን ብርቱ ምሥጢር ነበር ይሆን እንድል አድርጐኛል፡፡
የመጽሐፉ ድክመት
መጽሐፉ ከላይ በመጠኑም ቢሆን የነካካኋቸውን ጉዳዮች የዓይን ዕማኙን ሥዩም ጣሰውን ዋቢ አድርጐ የመቅረቡን ያህል ሌላ ድክመት እንዳለበትም መዘንጋት አያሻም፡፡
አሳታሚው በመግቢያው ላይ “አሽከር ሥዩም (አፈሩን ገለባ ያድርግለትና) በሰነዱ ውስጥ ጽሑፉን ለንባብ ሳያበቃው እንዳይሞት አምላኩን የተማጸነበት ፀሎት አለ” ብሎናል፡፡ ግን ይህንን ከሰነዱ ውስጥ አናገኘውም፡፡ ይህ የሚያሳየን የሥዩም ሰነድ የተነካካ ወይም የተቆራረጠ ፍሬ ነገር አለው ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ፍጹም ስህተት ነው፡፡ አንድ አካል ሲቆረጥ ሌላውን ምሉዕ እንደማያደርገው ሁሉ የሥዩም ጽሑፍም የቋንቋ አርትኦት ብቻ ተደርጐለት መታተም ነበረበት፡፡
ሌላው ከወሲብ፣ ከንዋይና ከሃይማኖታዊ ገመናቸው ይልቅ የንጉሱ ፖለቲካዊ ገመና ቢታከል ኖሮ ጽሑፉን ተወዳጅ ያደርገው ነበር፤ ሰዎችን በምሥጢር መግደልና ማስገደል፣ በፍርድ አካባቢ የነበረው ሸር ሁሉ ሊገለጽ በተገባ ነበር፡፡ ይህን አይነቱን ታላቅ ገመና ሥዩም ሳይነካካው አልቀረም፤ ግን በመጽሐፉ ላይ አናገኘውም፡፡ ይህ ደግሞ ታላቁንና ለ44 ዓመታት የኖሩበትን ገመና ምስጢር አድርጐብናል፡፡ ከገጽ 141 ጀምሮ እስከ ገጽ 172 ያለውና “ደም ያዘለ ዶሴ” ከሚለው መጽሐፍ እንዳለ ተገልብጦ የቀረበልንም የመጽሐፉ ትልቅ ድክመት ነው፡፡ እንደ ትርፍ አንጀት የተለጠፈውን 32 ገጽ ከዋናው መጽሐፍ “ደም ያዘለ ዶሴ” ላይ አንብበነዋል፤ እዚህ ላይ መደረቱ ለምን አስፈለገ?

Published in ጥበብ

       አንድ ቀን ሁለት ኢትዮጵያዊያን ጓደኛሞች እንደወትሮው ሻይ ቡና እያሉ ይጨዋወታሉ። በጨዋታቸው መሃል አንደኛው አንድ ሐሳብ ያመጣል፡፡ “ለምንድን ነው እኛ ሀገር ብዙ ሰዓሊያን የሚሣተፉበትና በርካታ የስዕል ስራዎች የሚቀርቡበት ፕሮግራም የማይዘጋጀው?” ሃሳቡን በጥሞና ያደመጠው የጥበብ አፍቃሪ፤ ከዚያች ሰዓት ጀምሮ የወዳጁን ትልቅ ሃሳብ እውን ለማድረግ ቆርጦ ተነሣ፡፡ የዚህ ሃሳብ አመንጪም “ይህን ታላቅ ሐገራዊ ስራ ከግብ ለማድረስ እኔም ሆንኩ የምመራው ድርጅት ካጠገብህ ሆነን እንደግፍሃለን” ሲሉ ቃል ገቡለት፡፡ እናም “Addis Art Fair” (አዲስ የጥበባት ትርኢት) ተወለደ፡፡
የዚህ ሃሳብ አመንጪ የደርባን ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሃይሌ አሰግዴ ሲሆኑ  ሃሳቡን ወደ ተግባር የለወጡት ደግሞ አርቲስት አበበ ባልቻ፤ ከዶ/ር ኤልሣቤጥ ወ/ጊዮርጊስ፣ ከረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን እና ከአለ የስነጥበባት ት/ቤት ጋር በመሆን ነው፡፡
ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2006 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ በታላቅ ድምቀት የተከፈተው “Addis Art fair” (አዲስ የጥበባት ትርኢት) በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ ለየት ያለ ነበር። የስነጥበብ ዓውደ ርዕዩ የተከፈተው በተለያዩ የኪነጥበብ ዝግጅቶች ታጅቦ ነው፡፡ ከ15ሺህ ሰው በላይ በሚይዘው የሚሌኒየም አዳራሽ፤ በመክፈቻው ዕለት የቀረበው የሲንፎኒ ሙዚቃ ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነበር፡፡ እምብዛም በሐገራችን ያልተለመደው የሲንፎኒ ሙዚቃ፤ በዚህ ግዙፍ አዳራሽ ውስጥ ጥራቱን በጠበቀ የድምጽ ስርዓት ሲንቆረቆር የብዙዎቻችንን ቀልብ ማርኳል፡፡ በተለይ ከሲንፎኒ ኦርኬስትራው ጀርባ ባለው ግዙፍ ስክሪን በርካታ ህፃናት ካሚዮን ላይ የሚፈልጉትን የስዕል ስራ ሲሰሩ የሚያሣየው ፊልም፣ ከሲንፎኒ ሙዚቃው ጋር ልዩ የጥበብ ህብር ፈጥሯል፡፡
100 የስነጥበብ ባለሙያዎች በተሣተፉበት በዚህ አውደርዕይ፤ ከ600 መቶ በላይ የስዕል፣ ቅርፃቅርፅ እና የዲዛይን ስራዎች ለዕይታ በቅተዋል፡፡ በ“አዲስ የጥበባት ትርኢት” ላይ የተሳተፉት የስነጥበብ ባለሙያዎች በሙሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ከዚህ ቀደም ስራዎቻቸውን ለተመልካች የማሣየት እድል ያላገኙ ሲሆኑ የተለያዩ ጋለሪዎችም ተሣታፊ ነበሩ፡ በዚህ ዝግጅት ላይ ከቀረቡት ስራዎች መካከል በቅርቡ ህይወታቸው ያለፈው የሰዓሊ ኤርሚያስ ማዘንጊያ እና የሰዓሊ ማቲያስ ሉሉ ውብ የጥበብ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የስነጥበብ ትርኢቱ በተለይ ለወጣት የስነጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ እድል የፈጠረ እንደ ነበር ብዙዎች መስክረዋል - ወጣት ሰዓሊያንን ጨምሮ፡፡ ስራዎቻቸው በጥበቡ አፍቃሪያን ከመጎብኘታቸውም ባሻገር የጥበብ ፍሬያቸውን በመሸጥ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሣድጉና ለተሻለ የጥበብ ስራ እንዲተጉ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡
በአገራችን ህብረተሰቡና የስነ-ጥበብ ስራው በእጅጉ የተራራቁ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን አዲስ አበባ በሚገኙ ጋለሪዎችና ሙዚየሞች እንዲሁም ሆቴሎች ውስጥ በሚዘጋጁ የስዕል አውደርዕዮች ላይ የተስፋ ብርሃን መፈንጠቅ ጀምሯል፡፡ በሚሌኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የጥበባት ትርኢት ላይ የተመልካች ጐርፍ ተመልክቼአለሁ፡፡ ለአራት ቀናት ክፍት ሆኖ የዘለቀውን የጥበባት ዓውደርዕይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጐብኝተውታል፡፡ በተለይ እኔ በሄድኩባቸው ሁለት ቀናት፣ በርካቶች በቡድን በመሆን እንዲሁም ቤተሰቦች ልጆቻቸውን እየያዙ የስነጥበብ ስራዎቹን ሲመለከቱ ታዝቤያለሁ፡፡ ተመልካች ስራዎቹን ተመልክቶ ከመሄድ በዘለለ ከሰዓሊያኑ ጋር የመወያየት ዕድል ማግኘቱንም አስተውያለሁ። በብዙ አውደርዕዮች የስነ-ጥበብ ስራዎችን ሲገዙ የሚታዩት የውጭ አገር ዜጎች ነበሩ፡፡ በሚሌኒየሙ “አዲስ አርት ፌር” ግን ብዙ ኢትዮጵያዊያን የጥበብ ሥራዎችን እንደገዙ ለማወቅችያለሁ፡፡ በእርግጥ የስነ-ጥበብ ስራዎቹ ዋጋ እንደሌላው ጊዜ የተሰቀሉ አልነበሩም፡፡ ከፍተኛው ዋጋ 8 ሺህ ብር ነበር፡፡ እንደ እኔ አተያይ የጥበብ ስራዎች ዋጋ ዝቅ መደረጉ፣ ኢትዮጵያዊያን በስነጥበብ ገበያ ውስጥ እንዲገቡ በር ከመክፈቱም ባሻገር ከጥበብ ሥራዎች ጋር የበለጠ ቅርርብና ትውውቅ እንዲፈጥሩም ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡
በቅርቡ ለንባብ የበቃው “African Business” መጽሔት፤ “Fortunes to be made from African Creativity” በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሑፍ፤ በርካታ የባህልና ጥበብ መፍለቂያ የሆነችው አፍሪካ ከመስኩ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳላገኘች ያትታል። መጽሔቱ እንደሚለው፤ የፈጠራ ኢንዱስትሪ ለዓለም ኢኮኖሚ 2.2 ትሪሊዮን ዶላር ወይም 7 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን እ.ኤ.አ በ2012 ብቻ ምዕራባዊያን 595 ቢሊዮን ዶላር ከኢንዱስትሪው አግኝተዋል፡፡ ከዚህ የትሪሊዮን ዶላር ገበያ የአፍሪካ ድርሻ ከአንድ ፐርሰንት በታች እንደሆነ የጠቆመው መጽሔቱ፤ አፍሪካ በባህልና ጥበብ ዙሪያ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት አትቷል፡፡ እንደ ሚሌኒየም አዳራሽ ዓይነት ዝግጅቶች ሳይቋረጡ በዘላቂነት ከቀጠሉ የሥነ ጥበብ ዘርፉ አስደናቂ እመርታ የሚያሳይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፡፡ ነፍሱን ይማረውና የ“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ መስራችና ባለቤት በነበረው በአቶ አሰፋ ጐሣዬ ፊታውራሪነት “Addis Art Week” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ አዲስ አበባን የነቀነቀው የጥበብ ዝግጅት በአርአያነቱ ዘወትር ይጠቅሳል፡፡
የሰሞኑን የጥበብ ትርኢት አስመልክቶ አስተያየቱን የሰጠው ሰዓሊ ዳዊት ገርሱ፤ ዝግጅቱ በዚሁ ከቀጠለ ነገ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ አለው፡፡ “አዲስ አርት ፌር በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ውስጥ በምስራቅ አፍሪካና በመላው አፍሪካ እንዲሁም በዓለም ላይ ደምቆ የሚታይ ትልቅ አቅም እንዳለው ያስተዋልኩበት ዝግጅት ነው” ብሏል፤ ሰዓሊው፡፡ የላፍቶ አርት ጋለሪ ኩሬተር ሰዓሊ ኑሩ አበጋዝ በበኩሉ፤ “ይህ የስነጥበብ ትዕይንት፤ የሐገራችንን የስነጥበብ ባለሙያዎች በእጅጉ የሚደግፍና የተዘበራረቀውን የስነጥበብ ገበያ ስርዓት ለማስያዝ የሚያስችል ነው።” ብሎ ያምናል፡፡ አውደርዕዩ በየአመቱ ሳይቋረጥ ይበልጥ እየደመቀ እንደ ሚቀጥልም ያልማል የሥነ ጥበብ ዝግጅቱን ለመጎብኘት የመጡ የክልል ተመልካቾች፤ “አውደርዕይው በሚዲያዎች በደንብ አልተዋወቀም፤ ከሳምንት በፊት ቀድሞ ቢነገር ብዙ የስነ-ጥበብ አድናቂዎች ይመጡ ነበር” ሲሉ አስተያየታቸውን ገልፀዋል፡፡ የጥበብ ትርዒቱ ለተመልካች ክፍት የተደረገበት ጊዜ በጣም አጭር ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አልጠፉም፡፡ አብዛኞቹ ግን ተመሳሳይ ስጋት ይጋራሉ፡፡ “አዲስ አርት ፌር በየዓመቱ ሳይቋረጥ ይካሄድ ይሆን?” የሚል፡፡
እኔ በበኩሌ፤ ይህ ረጅም ዓላማን ይዞ የተነሣ የጥበብ ዝግጅት፤ ነገ ከኢትዮጵያም አልፎ በአህጉር እና በአለም ደረጃ ትልቅ ስምና በርካታ ክንውኖች ያሉት ዓመታዊ ፕሮግራም እንደሚሆን ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡ የዘንድሮውን ዝግጅት ደፋ ቀና ብለው ለስኬት ያበቁት ሁሉ ምስጋና ሲያንሳቸው ነው፡፡ አሁንም በርቱ እላቸዋለሁ፡፡    

Published in ጥበብ

        የዓለም አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫዎችና በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ባገኙት የሽልማት ገቢ  ከ1 እስከ 50  በወጣው ደረጃ ኢትዮጵያ  በሁለቱም ፆታዎች  በ23 አትሌቶች እንደተወከለች ለማወቅ ተቻለ፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቶች በሽልማት ገቢያቸው ኃይሌ ገብረስላሴ እና ጌጤ ዋሚ ይመራሉ፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት  በዓለም ዙርያ በተካሄዱ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና ሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች አትሌቶች ያገኙአቸውን በግልፅ የሚታወቁ  የገንዘብ ሽልማቶች በመደመር ደረጃውን ከሳምንት በፊት  በድረገፁ ይፋ ያደረገው የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ማህበር (ARRS/ Associations of Road racing statisticians )  ነው፡፡ ይህን ዓለም አቀፍ ደረጃ  በወንዶች ምድብ  የሚመራው በ52 የተለያዩ ጊዜያት 3 ሚሊዬን 548 ሺህ 398 ዶላር ያፈሰው ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን በሴቶች ምድብ ደግሞ በ56 የተለያዩ ጊዜያት 2 ሚሊዬን 236 ሺህ 415 ዶላር ያገኘችው የእንግሊዟ ፓውላ ራድክሊፍ ናት፡፡  በወንዶች ምድብ በደረጃው ሰንጠረዥ መግባት ከቻሉት  50 አትሌቶች 10 ኢትዮጵያውያን ሲገኙበት በድምሩ 10 ሚሊዬን 345 ሺህ 423 ዶላር በሽልማት ገቢ አድርገዋል፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ  ከ50ዎቹ አትሌቶች 13 ያህሉ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ድምር የሽልማት ገቢያቸው 9 ሚሊዬን 575 ሺህ 957 ዶላር ነው፡፡
የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር www.arrs.net በተባለው ድረገፁ በዓለም አቀፍ
የአትሌቲክስ  ከ3ሺ ሜትር አንስቶ ያሉትን የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና ሌሎች ውድድሮች በትኩረት በመከታተል የአትሌቶችን የውጤታማነት ደረጃ፤ ሰዓትና ድምር ስኬት ከፋፍሎ በማስላት ወርሃዊ እና ዓመታዊ መረጃዎችን ይፋ ያደርጋል፡፡ በዚሁ ድረገፅ የዓለም አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫዎች እና በሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች በሰበሰቡት የሽልማት ገንዘብ ላይ ደረጃውን በማውጣት የሚያስታውቅበት አሰራርም አለው፡፡ ኤአርአርኤስ በሽልማት ገቢ  ለሚሰራው ደረጃ እና ሌሎች መረጃዎችን በድረገፁ ለማስፈር የሚጠቀምበትን ዳታቤዝ ለማዘጋጀት   በመላው ዓለም የሚደረጉን ከ160 ሺህ በላይ የጎዳና ላይ የሩጫ እና ሌሎች ውድድሮችን በመከታተል መረጃዎችን ከማሰባሰቡም በላይ በየውድድሩ  35 ሺህ አትሌቶች ያስመዘገቧቸውን 900 ሺህ በላይ ውጤቶች አገናዝቧል፡፡ እነዚህን መረጃዎች በማሰባሰብ እና በማቀናበር ከስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመላው ዓለም ያሉ ከ100 በላይ ባለሙያዎች የሚሰሩት ሲሆን  በሺዎች የሚቆጠሩ የአትሌቲክስ በጎ ፍቃደኞችም በተለያዩ ተግባራት ተሳታፊ ይሆኑበታል፡፡ ኤአርአርኤስ የዓለም አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫ እና ሌሎች የአትሌቲክስ ውድደሮች ያገኟቸውን የሽልማት ገቢዎች ያሰባሰበው በግል በሚመዘገብ ውጤት በግልፅ የሚወስዷቸውን የሽልማት ድርሻዎችና  በቡድን ውጤት የሚያገኙትን ገቢ በመደማመር ነው፡፡ በሽልማት ገቢው የተሰራው ደረጃ አትሌቶች በተለያዩ ዓለምአቀፍ ውድድሮች በግላቸው ተደራድረው የሚያገኟቸውን የተሳትፎ ክፍያዎች፤  ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞች፤ የቦነስ ሽልማቶች፤ የስፖንሰር ገቢዎች፤ እንደመኪና አይነት የተለያዩ ስጦታዎችን ያካተተ አይደለም፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው በኤአርአርኤስ ድረገፅ በዓለም አትሌቶች የሽልማት ገቢ ደረጃ ላይ በሁለቱም ፆታዎች ከ50ዎቹ ተርታ የገቡት የኢትዮጵያ አትሌቶች ባገኟቸው የሽልማት ገቢዎች በአገር እና በዓለምአቀፍ የሚኖራቸው ደረጃ ነው፡፡
=======================
በወንዶች
$3,548,398  (52)  ኃይሌ ገ/ስላሴ
                                                 - ከዓለም 1ኛ
1,559,828   (47) ቀነኒሳ በቀለ - 2ኛ
1,544,520   (18) ፀጋዬ ከበደ - 4ኛ
648,500   (10) አዲስ አበበ   - 15ኛ
$573,445   (24) ሌሊሳ ዴሲሳ  - 21ኛ
568,947   (38)  ገብሬ ገ/ማርያም - 22ኛ
533,700   (32) ድሪባ መርጋ - 26ኛ
475,850   (31) ታደሰ ቶላ- 35ኛ
475,465   (26) ጥላሁን ረጋሣ  -36ኛ
416,770   (11) ደሬሳ ኤዴ - 47ኛ

በሴቶች
$1,438,280   (44) ጌጤ ዋሚ   - ከዓለም 6ኛ
1,254,395   (67) ብርሃኔ አደሬ  - 9ኛ
970,893   (56)  መሠረት ደፋር  - 16ኛ
904,836   (43) ጥሩነሽ ዲባባ   - 17ኛ
835,605   (45)  ማሚቱ ደሳካ  - 19ኛ
772,189   (19) አሰለፈች መርጊያ  -  22ኛ
647,873   (46) ደራርቱ ቱሉ  - 28ኛ
622,053   (36) ድሬ ቱኔ አሪሲ  - 29ኛ
621,508   (25)  ብዙነሽ በቀለ  - 30ኛ
517,380   (40)  መሰለች መልካሙ   - 36ኛ
517,220   (18)  ትርፌ በየነ  - 37ኛ
515,185   (27) አፀደ ባይሳ  - 40ኛ
475,920  (29)  ሙሉ ሰቦቃ -  45ኛ
ማስታወሻ - በቅንፍ የተቀመጠው አኃዝ የተሸለሙበት ብዛት ነው፡፡
አንድ ዶላር በወቅታዊ የምንዛሬ ዋጋ 19.80 ብር ነው፡፡

          የዋልያዎቹን  ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የተከተለው የአሰራር ሂደት ከዓለም አቀፍ ልምዶች አንፃር እንደዘገየ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በብዙ የዓለም አገራት የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኞች ቅጥር ቢያንስ በ4 ቢበዛ በ5 ሳምንታት ውስጥ የሚፈፀም ቢሆንም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚሆን ዋና አሰልጣኝ አፈላልጎ ለመቅጠር እስካሁን 8 ሳምንታት ቢያልፉም ሂደቱ አልተጠናቀቀም፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለዋና አሰልጣኙ ቅጥር  ካወጣው ማስታወቂያ  በኋላ ለሁለት ሳምንት   ምዝገባ ተካሂዶ ከመላው ዓለም 27 አሰልጣኞች ያመለከቱ ሲሆን የስም ዝርዝራቸውና ዜግነታቸው ከሳምንት በፊት ታውቋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በመስፈርቶቹ 27ቱን አሰልጣኞች በማወዳደር ሲሰራ 1 ሳምንት ያለፈው ሲሆን የመጨረሻ እጩዎችን  ማንነትና ብዛታቸውን አልገለፀም፡፡  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የሚረከበው አዲሱ አሰልጣኝ መቼ  እንደሚታወቅ ፤  የቅጥሩ  ውል እንዴት እና መቼ እንደሚፈፀም፤ ለምን ያህል ግዜ በሃላፊነቱ እንደሚቆይ፤ ምን ያህል ወርሃዊ ደሞዝ እንደሚከፈለውና ፌደሬሽኑ ክፍያውን እንዴት ሊከፍል እንዳሰበም በይፋ የታወቀ ነገር የለም፡፡
የፌደሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ከሳምንት በፊት ለመገናኛ ብዙሃናት በላከው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን ፍላጎት ያሳዩ አሰልጣኞች ከመላው ዓለም ከሚገኙ 15 አገራት የተሰባሰቡ ናቸው ፡፡  ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከቤልጅዬም፣ከቱርክ፣ ከቦስኒያ፣ ከስፔን እና ከቡልጋርያ ከእያንዳንዳቸው አንድ አሰልጣኝ፤ ከጣሊያን፣ከኢትዮጵያ፣ ከስዊድን፣ ከሆላንድ፣ ከሰርቢያ፣ ከፖርቱጋል፣ ከብራዚል እና ከሮማኒያ ከእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት አሰልጣኞች እንዲሁም ከአርጀንቲና ሶስት አሰልጣኞች አመልክተዋል፡፡ እነዚህ አመልካች 27  አሰልጣኞች  በቅጥሩ ለመወዳደር ለፌደሬሽኑ ያስገቡት የስራ ልምድ እና ብቃትን በዝርዝር ባይገለፅም በእግር ኳስ ዙርያ መረጃ በሚገኝባቸው ድረገፆች ስለ ስራ ታሪካቸው ብዙ እውቅና ያላቸው ገሚሱ ናቸው፡፡  ስለ አሰልጣኞቹ መረጃ ማግኘት የተቻለው አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ ከመስራታቸው በተያያዘ፤ አንዳንዶቹ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ስላላቸው የስራ ልምድ በተለያዩ ድረገፆች ግለታሪካቸው ተፅፎ በመገኘቱ ነው፡፡  ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ክለቦችን በማሰልጠን ልምድ ኖሯቸው ለዋናው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ማመልከቻ ያስገቡት የደደደቢት አሰልጣኝ የነበሩት የቱርኩ ሜሜት ታይፉን እና አሁን የመብራት ኃይል ክለብ አሰልጣኝ ሆነው የሚሰሩት የቡልጋርያው ሎርዳን ስቶይኮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን አሰልጥነው የሚያውቁት እና በድጋሚ ቡድኑን ለመረከብ ያመለከቱት ደግሞ የጣሊያኑ ዲያጎ ጋርዚያቶ እና የቤልጅዬሙ ቶም ሴንትፌይት ናቸው፡፡ ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌይት ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ቅጥር ሳይፈፀምላቸው ለሙከራ እንዳሰለጠኑ የሚታወስ ሲሆን አሁን ብሄራዊ ቡድኑን ለመረከብ ከሁሉም ቀድመው ፍላጎታቸውን በሱፕር ስፖርት በመግለፅ የሚጠቀሱ ሆነዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት መግለጫ  እንዳመለከተው የቅጥር ማመልከቻቸውን ካቀረቡት 27 እጩ አሰልጣኞች መካከል ኢትዮጵያዊያን የሆኑት ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ የመጀመርያው ከ3 የውድድር ዘመናት  በፊት በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አሰልጣኝነት  የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው እና አሁን በሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ሼንዲ በረዳት አሰልጣኝነት በመስራት ላይ የሚገኘው ውበቱ አባተ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ አስቀድሞ በስኮትላንዳዊው ኢፌም ኦኑራ የዋና አሰልጣኝነት ዘመን  የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የፉትቦል ዲያሬክተር ሆኖ የሰራውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የአሰልጣኝነት ትምህርት የተከታተለው ዮሃንስ ተሰማ ናቸው፡፡  በአውሮፓ ታዋቂ ክለቦች ተሰልፈው ውጤታማ ከመሆን አልፈው በአውሮፓ፣ በአፍሪካና፣ በእስያ የሚገኙ ብሔራዊና ወጣት ቡድኖችን እንዲሁም ክለቦችን በማሰልጠን ለሻምፒዮንነት ክብር የበቁ ሙያተኞች  እንዳመለከቱ የገለፀው የፌደሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ፤ ብሄራዊ ቡድኑን ተረክቦ ለውጤት ለማብቃት ያላቸውን ፍላጎት በተለያያ መንገድ መግለፃቸው የሚያበረታታ ነው ብሏል፡፡ ከእጩ አሰልጣኞቹ መካከል ከ30 ዓመታት በላይ የማሰልጠን ልምድ ያላቸው፤ በዓለም አቀፍ ውድድሮች አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ እንደሚገኙበት የተገለፀ ሲሆን የጥቂቶቹ የትምህርት ዝግጅት በዲፕሎማ ከመወሰኑ በስተቀር አብዛኞቹ ከመጀመሪያ ዲግሪ በላይ ያላቸው፤ በአውሮፓው እግር ኳስ ማህበር የመጀመሪያ ደረጃ የአሰልጣኝነት ብቃት ማረጋገጫ የያዙና የፕሮፌሰርና የኢንስትራክተርነት ማዕረግ የተሰጣቸው ሙያተኞች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡  
የእግር ኳስ ፌደሬሽን ብሄራዊ ቡድኑን  ባለፈው 2 ዓመት ከ6 ወር በዋና አሰልጣኝነት የመሩትን ሰውነት ቢሻው  በተሻለ ለመተካትና ለውጥ ለመፍጠር በሚል ካሰናበተ ሁለት ወር ቢሆነውም በምትክነት ለመቀጠር ማመልከቻ ካስገቡት 27 አሰልጣኞች በስራ ልምዳቸው አለመሻላቸውን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ፤ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ለሚደረገው የመጨረሻ ማጣርያ ምእራፍ ለመገባት ከበቁ 10 የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ ለመሆን የበቃ፤ በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ወይም ቻን ውድድር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈ፤ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከዓመቱ ምርጥ ሶስት ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በሃላፊነት ለመረከብ ካመለከቱት 27ቱ አሰልጣኞች መካከል ስፖርት አድማስ የተወሰኑትን ለማስተዋወቅ ከዚህ በታች ያለውን አጭር መግለጫ አቅርቧል፡፡ እነዚህን አስር 10 አሰልጣኞች ለስፖርት አፍቃሪው ማስተዋወቅ የተቻለው ስለባለሙያዎቹ የሚገልፁ በቂ መረጃዎችን በተለያዩ ድረገፆች  በማፈላለግ ማግኘት ስለተቻለ ነው፡፡


ፋቢዮ ሎፔዝ የ50 ዓመት ጣሊያናዊ ናቸው። በትልልቆቹ የጣሊያን ሴሪኤ ክለቦች አትላንታና ፌዬሬንቲና በአማካሪነት አገልግለዋል፡፡ ከ2007 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለ6 የውድድር ዘመናት ከ6 በላይ የዝቅተኛ ሊግ ክለቦችን ያሰለጠኑ ሲሆን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ብዙም ልምድ የላቸውም፡፡


ሃንስ ሚሸል እድሜያቸው 49  ሲሆን በዜግነታቸው ጀርመናዊ ናቸው፡፡ በተጨዋችነት ዘመናቸው ግብ ጠባቂ ነበሩ፡፡ ከ2001 እ.ኤ.አ ጀምሮ ወደ ማሰልጠን ስራ ገብተዋል፡፡ በአሰልጣኝነት ስራ ዘመናቸው በቻይና ሀ-20 ቡድን ረዳት አሰልጣኝ፣ ከ2007 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለ3 ዓመት በሩዋንዳ  እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ዲያሬክተር፣ በ2011 የፊልፒንስ ሀ-25 ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ከተቀጠሩ በኋላ አድገው ባለፉት 3 ዓመታት ደግሞ የዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ በስፖርት ሳይንስና በማኔጅመንት ባችለር ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በታላላቆቹ የዓለማችን ክለቦች ሪያል ማድሪድ፣ አርሰናል፣ ካይዘስላውተርን፤ ሪቨር ፕሌት ሌሎችም  በአሰልጣኝነት የስራ ልምምድ በመስራት አስደናቂ ልምድ አላቸው፡፡



ዲያጐ ጋርዚያቶ በትውልድ ፈረንሳዊ ቢሆኑም በዜግነት ጣሊያናዊ ናቸው፡፡ አሁን የ64 ዓመት አዛውንት የሆኑት እኝህ አሰልጣኝ በተጨዋችነት ዘመናቸው የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ነበሩ፡፡ ከ1984 እ.ኤ.አ ጀምሮ በአሰልጣኝነት ማገልገል ሲጀምሩ የፈረንሳይ ዝቅተኛ ሊግ ክለቦችን ሲያሰለጥኑ ቆይተው ትልቁን ኃላፊነት የተረከቡት በ2001 እ.ኤ.አ ላይ የኢትዮጵያ ሀ 20 ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ሲመደቡ ነበር። በዚሁ ጊዜም የኢትዮጵያን ወጣት ቡድን በአርጀንቲና ለተደረገው 14ኛው የዓለም ወጣቶች ዋንጫ እንዲሳተፍ አብቅተዋል። የኢትዮጵያ ሀ-20 ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ከለቀቁ በኋላ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በክለብ ደረጃ ሲሰሩ ቆይተው በ2007 እ.ኤ.አ ላይ የቶጐ ብሔራዊ ቡድን ተረክበው ነበር፡፡ በቶጎ አሰልጣኝነት የቆዩት ግን ለ2 ወራት የስራ ጊዜ ነበር፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ትልቅ ውጤት በማስመዝገብ የተደነቁ ሲሆን ለሁለት ጊዜያት ያሰለጠኑትን የዲ ሪፖብሊክ ኮንጎውን ቲፒ ማዜምቤ  በ2009 እ.ኤ.አ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ እንዲያሸንፍ አድርገዋል፡፡ በ2012 እ.ኤ.አ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮትጵያ ተመልሰው በነበረ ጊዜ ዋና ብሔራዊ ቡድኑን በሃላፊነት ቢይዙም በአወዛጋቢ ሁኔታዎች ቢይዙም ከ2 ወራት በኋላ ተሰናብተዋል፡፡



ኤርኒስት ብራንድተስ የ58 ዓመቱ ሆላንዳዊ በተጨዋችነት ዘመናቸው የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ነበሩ፡፡ በሆላንድ ብሔራዊ ቡድን ከ1977 -85 እኤአ በመጫወት ልምድ ከማግኘታቸውም በላይ በ1978 እ.ኤ.አ ላይ አርጀንቲና ባስተናገደችው ዓለም ዋንጫ ለመጫወት የበቁ ናቸው፡፡ ከ1993 እ.ኤ.አ ወዲህ በአሰልጣኝነት ማገልገል የጀመሩ ሲሆን በተለይ በትልቁ የሆላንድ ክለብ ፒኤስቪ አይንድሆቨን በረዳት አሰልጣኝነት ለ9 ዓመታት ሰርተዋል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የተወሰነ የስራ ልምድ ያላቸው ሲሆን ለ2 ዓመታት የሩዋንዳውን ክለብ ኤፒአር ካሰለጠኑ በኋላ ባለፈው ዓመት ደግሞ የታንዛኒያው ክለብ ያንግ አፍሪካንስ አሰልጥነው ነበር፡፡


ዞራን ፍሊፖቪች የ69 ዓመቱ ፖርቱጋላዊ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ በተጨዋችነት ዘመናቸው ከሚጠቀስ ታሪካቸው ከ1970-78 በዩጎዝላቪያ ብሄራዊ ቡድን የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ሆነው ማሳለፋቸው ነው። በአሰልጣኝነት ስራ የጀመሩት በ1988 እ.ኤ.አ ጀምሮ ሲሆን ለ2 ዓመት የፖርቱጋሊ ትልቅ ክለብ ቤነፊካ አሰልጣኝ ሆነው ከመስራታቸው በላይ በ1999 እኤአ በጣሊያኑ ክለብ ሳምፕዶርያም አገልግለዋል።  ከዚያም ተጫውተው ወዳሳለፉበት ታዋቂው ክለብ ስታር ቤልግሬድ በመመለስ ለ3 ዓመት በአሰልጣኝነት አገልግለው በ2007 እ.ኤ.አ  የሞንቴኔግሮ ቡድንን በመምራት  ለ2 ዓመት አገልገለው ከዚያ ወዲህ  ስራፈት ናቸው፡፡

ጐራን ስቴቫኖቪች የ47 ዓመቱ ሰርቢያዊ በተጨዋችነት ዘመናቸው የአማካይ መስመር ተሰላፊ ነበሩ፡፡ ከ1983 ጀምሮ ለስምንት አታመት ለፓርቴዝያን ቤልግሬድ የተጫወቱ ሲሆን በ1985 እ.ኤ.አ የዩጐዝላቪያ ብሔራዊ ቡድን አባል ነበሩ፡፡ ከ2001 እ.ኤ.አ ወዲህ በአሰልጣኝነት መስራት ጀምረው ከ2003-2006 እ.ኤ.አ የሰርቢያና ሞንቴኔግሮ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ካገለገሉ በኋላ በ2009 እ.ኤ.አ ላይ በቀድሞ ክለባቸው ፓርቴዝያን ቤልግሬድ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ተቀጥረዋል፡፡ በ2013 ደግሞ በዚሁ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአፍሪካ ልምድ ያላቸው ሲሆን በ2011 እ.ኤ.አ ላይ የጋና ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠን በደቡብ አፍሪካ በተደረገው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈዋል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የቻይና ሱፕር ሊግ ክለብ በሃላፊነት ተረከበው የነበረ ቢሆንም ክለቡ ወደ ዝቅተኛ ሊግ በመውረዱ ተሰናብተው ያለፉትን ወራት ያለ ስራ ቆይተዋል፡፡


ስቴፈን ኮንስታንቲን የ51 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ከ1994 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለአሰልጣኝነት እየሰሩ ናቸው፡፡ 4 ብሔራዊ ቡድኖችን ለማሰልጠን ከሌሎቹ አመልካቾች የላቀ ልምድ ያላቸው ሲሆን  በ1999 እ.ኤ.አ ለሁለት ዓመት ኔፓልን፣ ከ2003 ጀምሮ ለ3 ዓመታት ህንድን፣ ከ2007 ጀምሮ ለአንድ ዓመት ማላዊን እንዲሁም በ2011 የሱዳን ብሔራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት መርተዋል፡፡ በአሰልጣኝነት የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሮፌሽናል ፍቃድ ያላቸው ሲሆን በስነልቦና እና በአካል ብቃት ስልጠና ምርጥ ተብለው ሁለት ጊዜ የተሸለሙ፤ በምግብ ሳይንስ ዲፕሎማ ያላቸው እና የአሰልጣኞች አሰልጣኝ ተብለው በፊፋ እውቅና ያላቸው ኢንስትራክተር ናቸው፡፡

“በህይወቴ እንደ ፎቅና ሊፍት የምጠላው ነገር የለኝም”

ከአለም ህዝብ ከ10 በመቶ በላይ የፎቢያ ተጠቂ ነው
ሴቶች ከወንዶች ሁለት እጥፍ ያህል በፎቢያ ይጠቃሉ

          ከፍ ያሉ ሥፍራዎችን የመፍራት ችግር (ፎቢያ) እንዳለበት ያወቀው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ የመማሪያ ክፍላቸው ወደሚገኝበት 3ኛ ፎቅ ለመሄድ ገና ደረጃዎችን መውጣት ሲጀምር ሰውነቱ ይንቀጠቀጣል፣ ልቡ በሃይል ይመታል፣ ፍርሃት ፍርሃት ይለዋል። ይህ ነገር በጊዜ ሒደት ሊተወው እንደሚችል ቤተሰቦቹም ሆኑ ጓደኞቹ ቢነግሩትም እሱ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩ እየባሰበትና ለከፍታ ቦታዎች ያለው ፍራቻ እየጨመረ ሄደ፡፡
እጅግ በበዛ ችግርና ፈተና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ለከፍተኛ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ቆይታውም በበርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች የተሞላ ነበር፡፡ የመማሪያ ክፍሎቹ በህንፃዎች ፎቅ ላይ መሆናቸው በየዕለቱ በትምህርት ገበታው ላይ እንዳይገኝና ትምህርቱን በአግባቡ እንዳይከታተል  እንቅፋት ሆነውበታል፡፡ ፍርሃቱ እጅግ የበዛ ቀን ሲቀር፣ ከመምህራኖቹ የሚደርስበት ተከታታይ ማስጠንቀቂያ ሲያደፋፍረውና እንደምንም አይኑን ጨፍኖ ወደ ክፍሉ ሲገባ የአራት አመታት የዩኒቨሲቲው ትምህርት አልቆ ወጣ፡፡
በኢትዮ ቴሌኮም የአይቲ ዲፓርትመንት ክፍል የተቀጠረው ከዩኒቨርሲቲው ከወጣ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር፡፡ በተማረው ሙያና በሚወደው የሥራ መስክ መሰማራቱ እጅግ ቢያስደስተውም ያ ከልጅነቱ ጀምሮ  ፈተና የሆነበት ልክ ያጣ የከፍታ ፍራቻ እዚህም ተከትሎት መጣ፡፡ ወደ ቢሮው ለመሄድ ገና ከቤቱ ሲወጣ ሃሣብ የሚሆንበት ባለስምንት ደረጃዎቹን ፎቅ መውጣት ነበር፡፡
ቢሮው የሚገኘው እጅግ ዘመናዊ አሳንሰር ከተገጠመላቸው የከተማዋ አዳዲስ ህንፃናዎች በአንዱ ላይ በመሆኑ ሊፍት የመጠቀም ዕድል ቢኖረውም ለአንዲትም ቀን ሞክሮት አያውቅም። “ሊፍት ውስጥ ገብቼ በህይወት የምወጣ አይመስለኝም፡፡ የሊፍቱ በር ጭርሱኑ የሚከፈት ሁሉ አይመስለኝም፡፡ በደረጃ ስወጣ እንኳን ዘወር ብዬ የመጣሁበትን ደረጃ ወደኋላ ማየት አልችልም፡፡ ህንፃው መስታወት በመስታወት ሆኖ ደረጃ እየወጣሁ መሬቱን ቁልቁል የማየው ከሆነ አዙሮኝ ልወድቅ ሁሉ እችላለሁ፡፡ በህይወቴ እንደፎቅና ሊፍት የምጠላው ነገር የለኝም፡፡ ይህ የፎቅና የደረጃ ፍራቻዬ ለትምህርቴም ለሥራዬም መሰናከል ሆኖብኛል፡፡ ትምህርቴን ለመቀጠል ወይም ደግሞ ሥራዬን ለመቀየር ፍላጐቱ ቢኖረኝም ይኸው ችግሬ እንደሚከተለኝ ስለማወቅ መድፈር አቅቶኛል፡፡ ይህንን ችግሬን ለማስወገድ የተለያዩ ሙከራዎችን ባደርግም አልተሳካልኝም፡፡ ሁሉም ቀስ እያለ ይተውሃል ይሉኛል፡፡ ይሄው 36 ዓመቴን አጠናቅቄአለሁ፡፡ መቼ እንደሚተወኝ አይገባኝ። በአውሮፕላን መብረር ስለማልችል በርካታ ስልጠናዎችና ልዩ ልዩ የውጭ አገር ዕድሎችን አጥቻለሁ፡፡ ችግሩ ካለበት ሰው ሌላ ማንም ስሜትሽን በቅጡ ሊረዳሽ አይችልም፣ ነገሩ ችግር ብቻ ሳይሆን በሽታም ነው፡፡ ሐኪም የማያድንሽ፣ ሰው የማያዝንልሽ በሽታ!”
 ይህንን ያለኝ በኢትዮ ቴሌኮም የአይቲ ዲፓርትመንት ክፍል በኃላፊነት ደረጃ ላይ ተመድቦ የሚሰራ አንድ ወጣት ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የተጠናወተው ከፍታ ቦታዎችን የመፍራት አባዜ (አክሮ ፎቢያ) ዕድሜው የወጣትነትን ድንበር እስኪሻገር ድረስም አልተወውም፡፡
ከልክ ያለፈ፣የተጋነነና ተጨባጭ የሆነ ምክንያት በሌለው ጉዳይ የሚፈጠር ስር የሰደደ ፍርሃት ፎቢያ ይባላል፡፡ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በዚህ ችግር የመጠቃት ዕድላቸው በሁለት እጥፍ እንደሚጨምር በእንግሊዝ ተመራማሪዎች የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ከዓለማችን ህዝቦች 10 በመቶ ያህሉ በአንድ የፎቢያ ዓይነት የመያዝ ዕድል እንደሚያጋጥማቸው የሚጠቁመው እ.ኤ.አ በ2012 የተደረገው ይኸው ጥናት፤ በተለይም ባደጉት አገራት ህዝቦች ላይ ጎልቶ እንደሚታይ አመልክቷል፡፡
ፍርሃት ሰዎች ራሳቸውን ከተለያዩ አደጋዎች እንዲጠብቁና ከችግሩ ለመከላከል የሚያስችላቸው ፈጣን ውሳኔ እንዲተገብሩ የሚያስጠነቅቅ ጤናማ ስሜት ሲሆን ከሰው ሰው በተለያዩ ሁኔታዎችና ደረጃዎች ሊገለፅ ይችላል፡፡ ይሄ ስሜት ጠንቃቃ እንድንሆንም ያግዘናል፡፡ ፎቢያ የሚሆነው ከጤናማው የፍርሃት መገለጫ በተለየ ያለአንዳች ምክንያት የሚከሰትና ቅጥ ያጣ ጭንቀትና መረበሽን የሚያስከትል ሲሆን ነው፡፡
ልዩ ልዩ ነገሮችን ያለምክንያት ከልክ በላይ የመፍራት አባዜ (ፎቢያ) በአራት ዋና ዋና ክፍሎች እንደሚከፈል የገለፀው ጥናቱ፤እነዚህም የደም ፍራቻ፣ የተፈጥሮ ሁኔታዎች ፍራቻ፣ የእንስሳት ፍራቻና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ፍራቻ እንደሚባሉም ጠቅሷል፡፡
ፎቢያ መነሻው ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ምክንያት እንደሌለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የሥነ ልቦና ባለሙያው ዶ/ር ተከተል ካሳሁን ይህንኑ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “የፎቢያ መነሻና ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው በግልፅ የሚቀመጡ ነገሮች የሉም፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ወደ ፎቢያነት ደረጃ ከመድረሱ በፊት የሚኖር ተራ ፍርሃት አለ፡፡ ለዚህ ፍርሃት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ምክንያቶች ደግሞ ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ - አንድ በልጅነቱ ሰው ከከፍታ ላይ ወይም ከፎቅ ላይ ተወርውሮ ሲወድቅ ያየ ሰው፣ ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ ለከፍታ ቦታዎች የሚኖረው ፍራቻ እያደገ ይሄድና ወደ ፎቢያ በመለወጥ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን አደጋ ላይ ሊጥልበት ይችላል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ፎቢያ ደግሞ ያለምንም ጥርጥር የህክምና እርዳታ ያስፈልገዋል” ብለዋል፡፡
በጣም የተለመዱና የበርካታ ሰዎች ችግር ከሆኑት ፎቢያዎች መካከል የከፍታ፣ የጨለማና የውሃ፣ ድልድይ የመሻገር፣ ፎቅ ላይ የመውጣት፣ በአውሮፕላን የመሳፈር፣ መኪና የመንዳት፣ ዳገታማ ቦታዎች ላይ (ፎቅ) ላይ የመውጣት፣ በሊፍት (በአሳንስር) የመሳፈር፣ መሰላል ላይ የመውጣትና ሰዎች በተሰበሰቡባቸው ቦታዎች ላይ የመገኘት  ፎቢያዎች ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ከፍታን የመፍራት ፎቢያ (አክሮፎቢያ)
ይህ አይነቱ ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች ዳገታማ ቦታዎች ላይ፣ ፎቅና መሰላል ላይ እንዲሁም ደረጃዎች ላይ መውጣትን አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ በሊፍት (በአሳንሰር) መውጣትና መውረድ ለእነዚህ አይነት ሰዎች የሞት ያህል አስፈሪ ነው፡፡ የከፍታ ፍራቻ ያለባቸው ሰዎች፣ በአውሮፕላን መሳፈርን አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ የዚህ ፎቢ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ድልድይ መሻገርንና መኪና ማሽከርከርንም ይፈራሉ፡፡ ፍራቻው  በአብዛኛው የፎቢያ ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን ችግሩ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን  በማወክ በተጠቂው ላይ ስነልቦናዊ ቀውስን ሊያስከትል ይችላል፡፡
የደም ፍራቻ (ሄማቶፎቢያ)
የዚህ ዓይነት ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች ደምን ጨምሮ ማናቸውንም ከደም ጋር ንኪኪ ያላቸውን ነገሮች የማየት ከፍተኛ ፍራቻ አለባቸው፡፡ መርፌ፣ ምላጭና የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ለእነዚህ ሰዎች ፍራቻ መነሻ ሊሆኗቸው ይችላሉ፡፡ ደም ባልሆነና ደም ሊሆን ይችላል ባሉት ነገር ሁሉ ፍርሃትና ድንጋጤ ይፈጠርባቸዋል፡፡
የማህበራዊ እንቅስቃሴ ፍራቻ (ሶሻልፎቢያ)
ይህ አይነቱ ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው ሥፍራዎች ላይ መገኘትን አጥብቀው ይፈራሉ። በሰዎች ፊት መብላት፣ መጠጣትና መናገርን ፈጽመው አይደፍሩም።  ምክንያታቸው ደግሞ በሥፍራው የተሰበሰቡት ሰዎች ስለነሱ የሚያወሩ ስለሚመስላቸው ነው። ይህ አይነቱ ጥልቅ ፍርሃት የሰዎችን ማህበራዊ እንቅስቃሴ የሚገድብና ከፍተኛ የሥነልቡና ችግር የሚያስከትል እንደሆነ የሥነ-ልቡና ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ የዚህ ችግር ተጠቂዎች እንደሠርግ፣ ለቅሶ፣ ግብዣ፣ ሃይማኖታዊ በአላት በሚከበሩባቸው ሥፍራዎችና ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች ላይ ጨርሶ መገኘት አይፈልጉም፡፡ ደህንነት የሚሰማቸው በፀጥታ ሥፍራ ብቻቸውን ሲሆኑ ነው፡፡
የእንስሳት ፎቢያ
በሰው ልጅ ላይ ምንም ጉዳት የማያደርሱ ወይንም የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ አነስተኛ የሆኑ እንስሳትን ጨምሮ ለማንኛውም እንስሳ ጥልቅ ፍራቻ ያድርባቸዋል - የዚህ ችግር ተጠቂዎች። ውሻ፣ ድመት፣ አይጥ፣ ሸረሪትና ጉንዳን እጅግ የሚያስፈሯቸው ሲሆን እነዚህን እንስሳት በተመለከቱ ጊዜ ወይንም በሌሉበት ሥፍራ ስማቸው ሲነሳ ከፍተኛ ፍርሃት ይሰማቸዋል፡፡ ይህ ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች በአብዛኛው ለችግሩ መነሻ የሆኑ ምክንያቶች ይኖሯቸዋል፡፡ በልጅነታቸው በእንስሳ የመነከስ ወይም ሌሎች ጉዳቶችን የሚያደርስ አደጋ ከገጠማቸው እስከ ዕድሜያቸው ፍፃሜ ድረስ እነዚህን እንስሳት ሲፈሩና ሲሸሹ ይኖራሉ፡፡  
የጨለማና የውሃ ፎቢያ
የዚህ ፎቢያ ተጠቂዎች ለጨለማ ወይንም ለውሃ ያላቸው ፍራቻ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ብርሃን በሌለባቸው ቦታዎች ላይ መንቀሳቀስም ሆነ ጨለማ በሆኑ ሥፍራዎች ላይ መገኘትን ፈፅመው ይፈራሉ። የጨለማ ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች፣ በአብዛኛው የከባድ ራስ ምታት ተጠቂዎች ናቸው፡፡ የውሃ ፎቢያ ተጠቂዎችም በተለይ ብቻቸውን ሆነው ውሃ ባሉባቸው አካባቢዎች መዘዋወርን አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ አነስተኛ ኩሬዎች ወይንም የውሃ መውረጃዎች ለእነዚህ ሰዎች ፍርሀት መነሻዎች ናቸው፡፡ ችግሩ ባስ ያለባቸው ሰዎች ደግሞ ለብቻቸው ሰውነታቸውን መታጠብም ሆነ ዋና መዋኘት ፈፅመው አይደፍሩም፡፡
የፎቢያ ተጠቂነት በምን ይገለፃል?
አንድ ሰው የፎቢያ ተጠቂ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ሰውየው ለነገሮች እጅግ የተጋነነ እና ቅጥ ያጣ የፍርሀት ስሜትን የሚያሳይ፣ ስሜቱ በእጅጉ የሚረበሽ፣ ውጥረት የሚያጠቃው፣ እንዲሁም ከሥፍራው ለመራቅ ወይም ለመሸሽ ጥረት የሚያደርግ ከሆነ የፎቢያ ተጠቂ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
የፎቢያ ችግር በህክምና ሊድን ይችላል?
የፎቢያ ችግር በህክምና እርዳታ ሊድን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ግን ራሱ የፎቢያ ተጠቂው  ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አንድ የፎቢያ ተጠቂ የሆነ ሰው ችግሩን የሚፈጥርበትን ነገር እንዲጋፈጠውና ውስጣዊ የፍርሃት ስሜቱን በማስወገድ፣ ፍርሀቱ ምክንያታዊ መሆን አለመሆኑን አጥብቆ መጠየቅና ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ የከፍታ ፍራቻ ያለበት ሰው፣ ሌሎች በደረጃዎችም ሆነ በአሳንሰር (ሊፍት) በመጓዛቸው ምክንያት የገጠማቸው ችግር አለመኖሩን በማየት፣ አዕምሮው ለፍርሃቱ ምላሽ እንዲሰጥና ጉዳዩ ምንም ችግር እንደማያስከትልበት እንዲነግረው ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ የችግሩ ተጠቂ ከነገሮች ጋር ቀስ በቀስ እንዲላመድና በውስጡ ያለው የፍርሃት ስሜት በሂደት እንዲወገድ ለማድረግ ያስችለዋል፡፡ ስር የሰደደና በራሱ በችግሩ ተጠቂ ጥረት ሊወገድ ያልቻለውን የፎቢያ አይነት ለማስወገድ የሚረዳ “ኮግኒቲቭ ቢሔቨየራል ቴራፒ” የሚባል የህክምና ዘዴ ያለ ሲሆን ህክምናው የሚሰጠው በስነ-ልቦና ባለሙያዎች ነው፡፡

============

የፍራቻ (ፎቢያ) ዓይነቶች

የመብረቅ ፍራቻ - አስትራፎቢያ
የማስመለስ ፍራቻ - ኢሜቶፎቢያ
የወሲብ ፍራቻ - ጂኖፎቢያ
የብቸኝነት ፍራቻ - ሞኖፎቢያ
የአይጥ ፍራቻ - ሙሶፎቢያ
የጭለማ ፍራቻ - ኒክቶፎቢያ
የቁጥር ፍራቻ - ኒውሮፎቢያ
የእባብ ፍራቻ - ኦፊዲዮፎቢያ
የእሳት ፍራቻ - ፓይሮፎቢያ
የሞት ፍራቻ- ታናቶፎቢያ
የባቡር ፍራቻ - ሲዴሮድሮሞፎቢያ
የፀጉር ፍራቻ - ትሪቾፎቢያ
የመርፌ መወጋት ፍራቻ  - ትራይፓኖፎቢያ

Published in ዋናው ጤና

               መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም ታትሞ በወጣው ስመ ጥሩው የታይም መጽሔት ላይ ማይክል ሹማን የተባለ ጸሐፊ “Forget BRIC, meet PINEs” (የBRIC ሀገራትን፡- ብራዚል፣ ራሺያ፣ ህንድና ቻይናን እርሷቸውና የPINEs ሀገራትን፡- ፊሊፒንስ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ናይጄሪያና ኢትዮጵያን ተዋወቁ፡፡) በሚል ርዕስ የራሱን የኢኮኖሚ ትንታኔ ያቀረበበትን ጽሁፍ ለንባብ አብቅቷል፡፡
ፊሊፒንስ፣ ኢንዶኔዢያና ናይጄሪያ ይህን የማይክል ሹማንን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ትንታኔ ጽሁፍ አንብበው ምን እንደተሰማቸው ወይም ምን አይነት አስተያየት እንደሰጡ አላውቅም፡፡
ዘጠና ሚሊዮን ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱት ኢትዮጵያዊያን ያላቸው የቴሌቪዥን ቻናል አንድ ብቻ ነው፡፡ ይሄው አንድ ለእናቱ የሆነው መንግስታዊው “የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን” እና ሌሎች መንግስታዊና ለመንግስት ልዩ ቀረቤታ ያላቸው የዜና ማሰራጫዎች፣ የማይክል ሹማንን ጽሁፍ ያቀረቡት ከፍ ያለ ትኩረት በመስጠትና ከዋና ዋና ዜናዎቻቸው እንደ አንዱ አድርገው ነው፡፡
እነዚህ የዜና ማሰራጫዎች ለጽሁፉ ከሰጡት ትኩረትና ዜናውን ካቀረቡበት ሞቅ ያለ ስሜት አንፃር በመመዘን፣ ማይክል ሹማን በታይም መጽሄት ላይ ያቀረበው ወቅታዊ የኢኮኖሚ ትንታኔ ኢትዮጵያን አስደስቷታል ብለን ብንናገር ዋሾ ልንባል አንችልም፡፡
ማይክል ሹማን ያቀረበው ጽሁፍ በጥቂት አረፍተ ነገሮች አጥሮና ተጠቃሎ ሲቀርብ እንዲህ የሚል ነው። “ከዚህ በፊት BRIC በመባል የሚታወቁት ብራዚል፣ ራሺያ፣ ህንድና፣ ቻይና ሲያስመዘግቡት በቆዩት ከፍተኛ ፈጣን እድገት የድህረ አሜሪካን የዓለም ኢኮኖሚ በዋናነት ይቆጣጠሩታል ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡ ይህ ግምት አሁን አይሰራም፡፡ እነዚህ ሀገራት አሁን እያስመዘገቡት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከእነዚህ ሀገራት ይልቅ የPINE ሀገራት በሚል አዲስ ስም የወጣላቸው ፊሊፒንስ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ናይጄሪና ኢትዮጵያ በቀጣዩ የዓለም ኢኮኖሚ መድረክና ድህነትን በማስወገድ በኩል እጅግ ጠቃሚ ሚና መጫወት የሚችሉ ወሳኝ ሀገራት በመሆን ብቅ ብለዋል፡፡ ስለዚህ ዓለም የBRIC ሀገራትን ትቶ አዲሶቹን የPINE ሀገራትን ይተዋወቅ፡፡”
ማይክል ሹማን፤ በታይም መጽሄት ላይ ያቀረበው ጽሁፍ አንኳር ፍሬ ነገር ይሄው ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ማይክል ሹማን የBRIC እና የPINE ሀገራትን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ አስመልክቶ ያቀረበው ትንታኔ በርካታ አቃቂር ለማውጣት እድል የሚሰጥ አይደለም፡፡
ናይጄሪያ በአፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ ባለትልቅ ኢኮኖሚ ሀገርና በ2050 ዓ.ም ከዓለም አስር ታላላቅ ኢኮኖሚዎች አንዱ ለመሆን ትልቅ ህልም ያለመችና ይህንን ትልቅ ህልሟን እውን ለማድረግ ደፋ ቀና በማለት ላይ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡
ትናንትና ከትናንት ወዲያ የከፋ ድህነትን፣ ረሀብንና የእርስ በርስ ጦርነትን ለመላው ዓለም ለማሳየት ዓለማችን ከኢትዮጵያ የተሻለ ወይም ኢትዮጵያን የሚያስንቅ ማስታወቂያ አልነበራትም፡፡ ዛሬ እንዲህ አይነት ኢትዮጵያ የለችም፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትናንት የድህነት፣ የረሀብና የእልቂት ታሪኳን በፈጣን ኢኮኖሚ ባለቤትነት መቀየር ችላለች፡፡
ለአስራ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያውያንን አስከፊ ፍዳና ስቃይ ያስቆጠራቸውን የደርግን ወታደራዊ አስተዳደር በትጥቅ ትግል ያስወገደው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ድርጅት ላለፉት አስራ ስድስትና አስራ ሰባት ዓመታት ያህል የሚመራበት ዋነኛ የርዕዮተ ዓለም መስመሩ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” እንደሆነ ለሚመራቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች ይነግራቸው ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የርዕዮተ ዓለም መስመሩ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መሆኑ ቀርቶ “ልማታዊ መንግስት” እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ግን የኢህአዴግ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ልዩነቱ ጨርሶ አይታያቸውም፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የየእለቱን ህይወታቸውንና የሀገሪቱን ጠቅላላ የፖለቲካ የኢኮኖሚና፣ የማህበራዊ መስኮች በመቆጣጠር ረገድ የመንግስት እጅ እያደር ሲረዝም እንጂ ሲያጥርና ሲሰበሰብ ትናንትም ሆነ ዛሬ ለአፍታም እንኳ አይተው ስለማያውቁ ነው፡፡
በኢህአዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት፤ ላለፉት ዓመታት ያስመዘገበውን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይ በማድረግ በ2025 ዓ.ም ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ እቅድ ነድፏል፡፡ ለአምስት ዓመት እንዲሆን ተብሎ የተዘጋጀው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሊገባደድ አንድ ዓመት ብቻ ቀርቶታል፡፡ በዚህ እቅድ መገባደጃ ላይ ይገኛል ተብሎ የታሰበውን የአፕል ፍሬ ግን በረሮ ወሮታል። እንደ እውነት ከሆነ አለመጠን የረዘመው የመንግስት እጅ፣ የራሱ ዕቅድ እንዳይሳካ በራሱ በመንግስት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥሮበታል፡፡ በየትኛውም አይነት ርዕዮተ ዓለም ለሚመራ መንግስት የኢኮኖሚ እድገቱ እንዲሳለጥና የውጭም ሆነ የውስጥ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ከፈለገ፣ ጥራትና ብቃት ያለው አስተማማኝ የመሰረታዊ አገልግሎት መስጠት መቼውንም ጊዜ ቢሆን ግድ ነው። በኢትዮጵያ እንደ ውሀ፣ መብራትና፣ የቴሌኮሚኒኬሽን መገናኛን የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች መቶ በመቶ በመንግስት የተያዙ ናቸው፡፡
መንግስት እነዚህን አገልግሎቶች “የሚታለቡት ላሞች” በማለት ይጠራቸዋል፡፡ ነገር ግን አለመጠን የረዘመው የመንግስት እጅ እነዚህን ላሞቹን በሚገባ ማለብና ወተታቸው ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ከቶውኑም አልቻለም፡፡
ዛሬ መንግስት እነዚህን ወሳኝ የሆኑ መሰረታዊ አገልግሎቶች ለህዝቡ በወጉ ማቅረብ ተስኖታል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ኢትዮጵያዊያን ከአምላካቸው ቀጥሎ መንግስታቸውን በመፍራትና በማክበር ይታወቃሉ፡፡ መንግስታቸው እንዲፈጽሙት ያዘዛቸውን ማናቸውንም አይነት ትዕዛዝ ያለ ብዙ ማንገራገር ይፈጽማሉ፡፡ መንግስት በሚያወጣቸው ህጎች ጠማማነትና በአመራሩ ጉድለት የተነሳ ለከፍተኛ የኑሮ ጫናና የመብት ረገጣ ሲጋለጡ እንኳ በቅድሚያ የሚያደርጉት በአመጽ አደባባይ መውጣት ሳይሆን የተጫናቸውን ቀንበር እንዲያቀልላቸውና መልካም ጊዜን እንዲያመጣላቸው አምላካቸውን በፀሎት መማፀን ነው። ከዚህ ባለፈ በችግሮቻቸው ላይ በመቀለድ ራሳቸውን በመጠኑም ቢሆን ዘና ያደርጋሉ፡፡ መንግስታቸው ግን ይህንን እጅግ አስገራሚ ትዕግስታቸውን አብዛኛውን ጊዜ ነገሬ ብሎ ከጉዳይ ጥፎት አያውቅም፡፡
መንግስት አለቅጥ በተጠናወተው የቁጥጥር አባዜ የተነሳ፣ ከመጠን በላይ ያስረዘመው እጁ ያስገኘለት ትርፍ ቢኖር በአስደንጋጭ ሁኔታ እለት በእለት እየተንሰራፋ የመጣውን ንቅዘትና ሙስና ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እጅግ ኮሚክ የሆነው የመንግስት ነገር፣ ራሱ በረጅም እጁ የፈለፈላቸውን ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ በድኑ እንደመዋጋት ፈንታ ህዝቡን በታሰረ አንጀቱ ሞጥረህ ተዋጋልኝ ማለቱ ነው፡፡
ማይክል ሹማን በጽሁፉ እንደጠቀሰው፤ ናይጄሪያ በነዳጅ ዘይት ሀብት እጅግ የበለፀገችና ኢኮኖሚዋም በዋናነት በነዳጅ ዘይት ሽያጭ በሚገኝ ገቢ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ለምሳሌ ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ ብቻ 55 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች፡፡ የናይጄሪያን ነገረ ስራ ጉዳዬ ብለው በጥሞና የሚከታተሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግን እስኪ ናይጄሪያን በአንድ አረፍተ ነገር ግለፅዋት ሲባሉ፤ ዘና ብለው “ህዝቦቿ እጅግ ደሀ የሆኑ በጣም ሃብታም ሀገር” ሲሉ ይገልጿታል፡፡
ይህን እውነት ማንም ሀሰት ነው ብሎ መከራከር አይችልም፡፡ ለምን ቢባል አንድ መቶ ስልሳ ሶስት ሚሊዮን ከሚሆነው የናይጄሪያ ህዝብ አንድ መቶ አስር ሚሊዮን የሚሆኑት በቀን ከአንድ ዶላር በታች ገቢ በማግኘት ኑሮአቸውን ይገፋሉ፡፡
ናይጄሪያውያን በየዓመቱ ከነዳጅ ዘይት ከነሱ አልፎ ለሌሎች ሊተርፍ የሚችል ከፍተኛ ገቢ ማስገባት ቢችሉም አፕላቸው የበረሮ ሲሳይ ከመሆን አልፎ እነሱ እጅ ላይ ጠብ ለማለት አልቻለም፡፡ ናይጄሪያውያኑ ራሳቸው ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲጠየቁ “ገንዘባችንን ሰይጣኑ ስለሚበላብን ነው፡፡” በማለት አለአንዳች መሰልቸት ያስረዳሉ፡፡ ሰይጣኑ እያሉ የሚጠሩት ሙስናን ነው፡፡
ሙስናን በተመለከተ ኢትዮጵያውያን “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል!” የሚል እድሜ የጠገበ አባባል አላቸው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ያደጉት ይህን አባባል እየተናገሩ አሊያም ሲነገር እየሰሙ ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙስና በመላ ሀገሪቱ ከምን ግዜውም በበለጠ ሁኔታ ተንሰከፋ በማለት መንግስታቸውን ለአምላካቸው ያሳቅሉታል፡፡ እርስ በርስ ሰብሰብ ብለው ሲጫወቱም በሀሜት ይቦጭቁታል፡፡
ናይጄሪያውያን ደግሞ ሙስናን በተመለከተ፤ “ፀሐይዋ በደመቀች ጊዜ ድርቆሽህን አድርቅ!” የሚል አባባል አላቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ሆነ ናይጄሪያውያን እነዚህን ሀገርኛ አባባላቸውን በተግባር ላይ አላዋሉትም በማለት ራሱን እንደ ቂል የሚያስገምት ሰው አይገኝም፡፡ የአጠቃቀማቸውን መጠን በተመለከተ ግን ኢትዮጵያዊያኑን ከናይጄሪያውያን ጋር ማወዳደር በእርግጥም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡
“ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለውን አገርኛ አባባል እየተናገሩና እየሰሙ ያደጉት ኢትዮጵያዊያን፤ በቅርብ ጊዜ መንግስታቸው በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ጠርጥሮ ካሰራቸው የሀገሪቱ የግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ሳንዱቅ ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር (ሀምሳ ሁለት ሺ ዶላር) የሚጠጋ ገንዘብ መገኘቱን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲያዩ ተገርመውና ተደንቀው ነበር፡፡
የኢትዮጵያውያኑን መገረምና መደነቅ ያዩት ናይጄሪያውያን ደግሞ “ኢትዮጵያዊያን ሙስና ማለት ምን ማለት እንደሆነ በወጉ አልገባቸውም፡፡” ብለው በተራቸው ሲገረሙ,ኧ ኢትዮጵውያኑን የሙስና ተጠርጣሪዎች ደግሞ “አንድ ጠርሙስ ጥሩ ውስኪ ወይም አንድ ብልቃጥ ስም ያለው ሽቶ ለማይገዛ ብር አጓጉል ተልከስክሰው መንግስታቸውን ስራ አስፈቱት።” በሚል ተሳልቀውባቸዋል፡፡
እቅጩን እንነጋገር ከተባለ ናይጄሪያውያን እውነታቸውን ነው፡፡ የጅጋዋ ግዛት ገዢ ሆነው ባገለገሉበት ጥቂት ዓመታት ውስጥ 218.6 ሚሊዮን ዶላር መዝረፍ የቻሉ እነ ሳሚኑ ቱራኪን የመሰሉ አገረ  ገዥና ከ1993 እስከ 1998 አጋማሽ ድረስ ፕሬዚዳንት ሆነው ናይጄሪያን በመሩበት ወቅት አምስት ሚሊዮን ዶላር የዘረፉ ሳኒ አባቻን የመሰሉ ፕሬዚደንት ላሏቸው ናይጄሪያውያን ሀምሳ ሁለት ሺ ዶላር አይናቸው ውስጥ ቢገባም እንኳ ጨርሶ አይቆረቁራቸውም፡፡
በናይጄሪያ የተንሰራፋው ሙስና አቻ የለሽ መሆኑን ድፍን ዓለም አሳምሮ ያውቀዋል የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ ግን ሙስናን በተመለከተ በመላው ዓለም ናይጄሪያ የምትገኝበት ምድብ “የአሸናፊዎች አሸናፊ” ምድብ ውስጥ መሆኑን በሚገባ ያረጋገጠ ነው፡፡ የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ የነበሩት ላሚዶ ሳኑሲ፤ በመስከረም ወር ለፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን በፃፉት ደብዳቤ፤ የናይጀሪያ ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያ ከጥር ወር 2012 ዓ.ም እስከ ሀምሌ ወር 2013 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ፣ ለአለም ገበያ ካቀረበው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ስልሳ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ቢችልም ወደ ማዕከላዊ ባንኩ ገቢ የተደረገው ግን አስራ አምስት ቢሊዮን ዶላሩ ብቻ ነው፡፡ አርባ ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላሩ የት እንደገባ እስከዛሬ ድረስ ያወቀ ሰው ስላልተገኘ “ሰይጣኑ እንደበላው” ተቆጠረ፡፡  የዚህን ጉድ ጉዳይ በደብዳቤ ያሳወቁት ሳኑሲ ላሚዶና መሰሎቻቸው ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን የነገሩ ክብደት አስደንግጧቸው ጠንካራ እርምጃ ባፋጣኝ በመውሰድ እንዲያው ሌላው ቢቀር የተወሰነ ቢሊዮን ዶላር ከሰይጣኑ አፍ ማስጣል ይችላሉ ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡
በእርግጥም ፕሬዚደንት ጆናታን አፋጣኝ እርምጃ ወስደዋል፡፡ የወሰዱት እርምጃ ግን የናይጀሪያ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ የሆኑትንና ይህ አቻ የለሽ ሙስና መፈፀሙን በደብዳቤ በመግለጽ ተገቢውን እርምጃ ባፋጣኝ እንዲወስዱ ያሳሰቧቸውን ሳኑሲ ላሚዶን ከሃላፊነታቸው ማባረር ነው፡፡ ናይጀሪያ የነዳጅ ዘይት ያገኘችው በ1956 ዓ.ም ነው፡፡ እስከዛሬ ካገኘችው የነዳጅ ዘይት ገቢ ውስጥ 400 ቢሊዮን ዶላሩን ሰይጣኑ በልቶታል፡፡  

Published in ከአለም ዙሪያ
Page 5 of 17