Saturday, 15 March 2014 12:05

ሉሲፈር

            ሰሜን ሆቴል እና በዮሐንስ መሀል ላይ-ዳትሰን ሰፈር፡፡ የቀለጠው መንደር። ሰፈራችን በመጠጥ ቤት እጥረት አይታማም፡፡ ሄድ ሲሉ ቡና ቤቶች፣ እጥፍ ሲሉ ግሮሰሪዎች … ወረድ ቢሉ የአረቄ ቤት ድርድር … ጠምዘዝ ቢሉ ጠጅ ቤት፡፡
ጠጅ ቤት ተሰይሜያለሁ፡፡ አራተኛ ብርሌ ወደማገባደዱ ተዳርሻለሁ፡፡ … ሁለት ወጣቶች ገቡ፡፡ ከፊት ለፊቴ ተቀመጡ፡፡ የተቀዳላቸውን ጠጅ በፍጥነት ጭልጥ አደረጉ፡፡ ሌላ ብርሌ - ጭልጥ! ሦስተኛ ላይ ሰከን አሉ፡፡ ባቄላ አሰፍረው በመስገብገብ አሻመዱ፡፡
…አራት! አራት! ቅቅል እንቁላል ዋጥ ስልቅጥ አደረጉ፡፡ ጨዋታ ጀመሩ ልበል-አልዘለቁበትም፡፡ የፔርሙዝ ቡና የምትሸጠው ስትገባ ገቱት፡፡ ሁለት ሁለት ሲኒ ቡና ጠጡ፡፡ አፍታም ሳይቆዩ ሲጋራ ለኩሰው ይለመጥጡ ጀመር፡፡ የሲጋራው ጢስ በዙሪያቸው ተጉተለተለ፡፡ በዚያ የጭስ ጉም ሽንቁር፣ የአንደኛውን ልጅ እይታ ተከትዬ ሳማትር አይኔ ፀዳለ ላይ አረፈ፡፡ ፀዳለ አደገኛ ቀምቃሚ ናት። እግረ መንገዷን ቢዝነስ ትወጣለች። ልጁን ጠቀሰችው። እንደማግኔት ስባ ከጎኗ አስቀመጠችው። ጥቂት ተጨዋወቱ ልበል-ተያይዘው ወጡ፡፡
ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጠጅ-ባቄላ-ቅቅል እንቁላል-ቡና-ሲጋራ-ሴት! አቤት የአምሮት መዓት! ከዚያስ የትኛው አምሮቱ ያገረሽበት ይሆን?
ከቀረው ልጅ ጋር ወግ ጀመርን። ለሦስት ዓመት ወህኒ ወርደው ዛሬ መፈታታቸውን አጫወተኝ፡፡ … ሸምገል ያሉ እንግዳ ብርሌ አጣቢ ላይ አይኔ አረፈ። ግር አለኝ፡፡ ፍቃዱስ? … ጠጅ ቀጂውን ጠርቼ “ብርሌ አጣቢው ፍቃዱስ?”  
“ለመስቀል ሀገር ቤት ገባ፤ ጋሼ… ወጪውን ሁሉንም ነገር ችለው ላኩት።” … ፍቃዱን ቢያንስ ለአምስት ዓመት እዚሁ ጠጅ ቤት አውቀዋለሁ፡፡ ስለ ፍቃዱ ማንም ምንም አያውቅም፡፡ የትውልድ ሀገሬ እዚያ ነው - ከዚህ መጣሁ - ከዚህ ፈለስኩ - ሲል አይደመጥም፡፡ ጉራጌ መሆኑ ግምቴ ነው፡፡ ጥርት ባለ አነጋገሩ፡፡ መስቀል ብሎ ሀገር ቤት ገብቶ አያውቅም፡፡ ብርሌ አጣቢ የነበሩ ወደ ቀጂነት ደረጃ ከፍ ሲሉ፣ ፍቃዱ ከብርሌ አጣቢነት ፈቅ አላለም፡፡ ብርሌዎቹን እንደ መስተዋት ጥርት አድርጎ ማጠብ ከምንም ነገር በላይ ያረካኛል ይላል፡፡ ለብርሌዎቹ ልዩ ፍቅር አለው፡፡ በጠጅ ቤት አንባጓሮ ለምን ሰላሳ ሁለት ጥርስህ አይረግፍም ፍቃዱ ቅንጣት የሀዘኔታ ስሜት አይማውም፡፡ የአንድ ብርሌ መሸረፍ ግን ቱግ! አድርጎት፣ ሽራፊውን አንቄ ካልገደልኩ የሚል ሰው ነው፡፡ የመጨረሻዋን ብርሌ ጠጅ ጨለጥኩ፡፡ አስር ብር ከፍዬ ወጣሁ፡፡
“በዚህ የኑሮ ውድነት ጠጅ ባይኖር ምን እንጠጣ ነበር?”
 “መርዝ!”
መስከረም 17 ቀን 1999 ዓ.ም
መስቀልን አየር ጤና አክስቴ ቤት አሳለፍኩ። ደንገዝገዝ ሲል ወደ ሰፈሬ ለመመለስ ተነሳሁ፡፡ ታክሲ ከመያዜ በፊት አንድ ሁለት ብልስ ብዬ ግሮሰሪ ገባሁ። ደብል አፕሬቲቭ አዘዝኩ፡፡ ከውስጥ አንድ ሰው ወጣ-እንዴ ፍቃዱ! … እሱም ዞር ሲል እኔን በማየቱ ዱብዳ ሆኜበት በግርምት አፈጠጠብኝ፡፡ የምንተፍረቱን “ሰላም ነህ… በዓልስ?” ብሎ ወንበር ስቦ ከጎኔ ተቀመጠ፡፡ “ለመስቀል ገጠር የገባህ መስሎኝ?”  
“ከአመታት በኋላ ለመስቀል ገጠር ገባ የተባለው ብርሌ አጣቢ፣ አየር ጤና ገብቶ ስታገኘው ግር ይላል፡፡ ሁሉንም አጫውትሃለሁ፡፡” አለና ደብል ኡዞ አረቄ አዘዘ፡፡ … አልኮሉን በአንድ ትንፋሽ ጨለጠ። ፊቱን ልብ ብዬ አየሁት፡፡ እርጅና እና መታከት ታትሞበታል፡፡
“… በአስራ ስድስት ዓመቴ ነበር ከገጠር አዲስ አበባ መርካቶ የገባሁት። ሰባት ዓመት ልብስ ሰፊውን አጎቴን እየረዳሁ ሙያውን ተማርኩ፡፡ … አጎቴ በማረፉ የልብስ ስፌት መኪና እና ቤቱን ወረስኩ፡፡ በልብስ ስፌት ከራሴ አልፌ ለቤተሰብ ተረፍኩ…”
ኡዞውን ጨለጠ፡፡ እኔም ጨለጥኩት፡፡
“ዛሬም ቀኑ ትዝ ይለኛል፡፡ ጥር 15 ቀን 1980 ዓ.ም ሦስት ቀዘባ የመሰሉ የመንደሬ ልጃገረዶች ቤተሰብ ሊድራቸው ዳር ዳር ሲል ጠፍተው አዲስ አበባ መጡ። ያረፉት መርካቶ እኔው ዘንድ ነበር … ለገሃር በሚገኝ ገበያው የደራ ምግብ ቤት ዋስ በመሆን አስቀጠርኳቸው … በየወሩ ዕረፍት ሲወጡ በቀጥታ የሚመጡት እኔው ቤት ነበር … አንዷ እቃውን ታጥባለች፤ ሌላዋ ልብሴን… ሦስተኛዋ ምግብ ታዘጋጃለች … እናም ያንን የገጠር ውብ ሕይወት እያነሳን፣ እየበላን እየጠጣን መሳሳቅ ነው። … እንደዘበት አመታት ተቆጠሩ፡፡” አለና አረቄውን ጨለጠ፡፡ እኔም አፕሬቲቬን …
“በሆነ በዓል ከምግብ፣ ከመጠጡም ገደብ አልፈን ስንጯጯህ በመሀል ጤናዬ … “ሌላ ሴት አልያዝክ፤ ወጣት ነህ … እንዴት አንዳችንንም ለፍቅር አልጠየከንም … ይህን ያህል መልከ ጥፉ አይደለን… ወይንስ … ያ ነገር የለህም። ያለ መጠን የጋፈችው ፊልተር ጠላ፤ የሴትነት ይሉኝታዋን አሳጥቶ፣ ሆድ ያማውን ብቅል ያወጣዋል እንዲሉ… በንግግሯ ክው አልኩ፡፡ ውዴ እና የሺ፤ በጤናዬ ጋጠ ወጥ ጥያቄ ደንገጥ ቢሉም፣ የእኔን ምላሽ ለመስማት አፈጠጡብኝ፡፡ ምን ብዬ እንደምመልስ ግራ ገባኝ … በርግጥ ወጣት ነኝ፡፡ የ25 ዓመት ጉብል-የቀይ ዳማ ሰልካካ… አይናማ ወጣት…”
የዛሬውን ፍቃዱ ልብ ብዬ አስተዋልኩት። ተጨራምቶ የወየበ ፊቱ ጥንታዊ ብራና ይመስላል ልበል፡፡ “እንደ እህቶቼ እንደማያቸው ቀበጣጠርኩ … ያቺ እርጉም ጤናዬ ‘ድንቄም እህትነት! ባህታዊ አይደለህ! ለዚህም ነው ያ ነገር!” … አላስጨረስኳትም፡፡
“ጋጥ ወጥ አግድም አደግ ባለጌ ነሽ!” ስል ጤናዬ ላይ ደነፋሁ … እየተመናቀረች ወጣች፡፡ የሺ ልትመልሳት ተከተለቻት። ሁለቱም አልተመለሱም።”
“ውስጥ የቀረችው ልጅስ?”
“ውዴ! … ዛሬም እንደ ህልም ያ ትዕይንት ምትሀት ሆኖ ይታየኛል፡፡ ከጎና ተቀመጥኩ - ልጥፍ አለችብኝ፡፡ እርቃን የቀረ ጭኗ ላይ አይኔ ተጣበቀ። ቀና ስል አይኖቿ ተቀበሉኝ፡፡ የብርሃን ፀዳል ይረጫሉ፤ ያ የብርሃን ሞገድ ነዘረኝ፡፡ ጣዝማ መሳይ ማር አካሏ ላይ አጣበቀኝ፤ ንጥር ስሜቷን ያለ ንፍገት ጋበዘችኝ… ድንግል ነበረች” መጠጡን በፍጥነት ጨለጠ፡፡ የታሪኩንም አዙሪት በፈጣን ምላሱ አሾረው…
“በሳምንቱ የሺ ብቻዋን ቤቴ መጣች … ያውም በምሽት - ጉንጯን የምስም መስዬ ከንፈሯን መጠጥኩ - የወይን ዘለላ እንደ መምጠጥ ነበር … አንዳችም ተቃውሞ አላሳየችም - እንዴት በእርቃን እንደቀረን አላስታወስንም … ጡቶቿ መሀል ሟሟሁ - ከሰማይ ሰማያት በላይ በሩካቤ ሰረገላ ተንሳፈፍን - ከዋክብት ከሰሙ፤ እንደ አበባ ረገፉ - ብር አምባር ሰረበልዎ! ላቤ እንደ ጤዛ ኮለል ብሎ ወረደ - እንባዋ ገባር ወንዝ ሆኖ ተመመ”
… ደም፡፡ ላብ፡፡ እንባ፡፡ ፍቅር። የማላውቀው ንዴት ብልጭ አለብኝ። ግንባሩን በብርጭቆ ብበረቅሰው በወደድኩ፡፡ ፍቃዱ ትረካውን ቀጠለ …
“… ውዴና የሺ ድብብቆሽ የያዙ መሰለኝ፡፡ ሁሌም የሚመጡት ለየብቻ ነው፡፡ እንደበፊቱ የወር ፈቃድ ጠይቀው አንድ ላይ እየተንጋጉ መምጣቱን እርግፍ አድርገው ተውት፡፡ ጨዋታው በግል ሆኗል - የአልጋ ላይ ጨዋታ … እንዲህ በማፈራረቅ ለወራት ከሁለቱም ጋር ቀበጥኩ፡፡ … ከዕለታት በአንደኛው ቀን የሺህ “የወር አበባዬ ቀረ” ብላ ተንሰቅስቃ አለቀሰች … ዱብ ዕዳ ሆነብኝ፡፡ በየሺ እርግዝና ለሳምንታት ስጨነቅ ስጠበብ ውዴ አይኖቿ ቀልተው … ፊቷ አባብጦ “ሳልፀንስ አልቀርም-የወር አበባዬ? አለች”
“እንዴት ተደርጎ?”
“ያደረግነውንማ ታውቀዋለህ!”
የምይዝ የምጨብጠውን አጣሁ፡፡ በየተራ እየመጡ መነፋረቅ ሆነ … ቀናት እንደዘበት ነጎዱ … በዕለተ ሰንበት ሁለቱም አብረው መጡ፡፡ ባለማመን አፈጠጥኩባቸው … ሀቁን ተነጋግረው ነበር፡፡ በወሲብ የተለያየ ጓደኝነታቸው፣ እርግዝና አንድ አድርጓቸው … መላቀስ ሆነ፡፡
እኔም ሆድ ብሶኝ ለስንቱ ዘመድ የመጨረሻ መሰናበቻ የሚሆነኝን እንባ እንደ ጎርፍ አፈሰስኩት … ‘እሳትን በእንባህ ልታጠፋው አትችልም’ እንደሚባለው የሚበጀውን ተነጋገርን - ለማስወረድ … ሁለቱም ተስማሙ … በሳምንት ጊዜ ውስጥ ሁሉንም አጠናቅቄ እንደማሳውቃቸው ቃል ገባሁላቸው፡፡
ልምድ አለው የተባለው ዲረሰር በሰው በሰው አገኘሁ … በቀጠሮአችን ሁለቱንም ብጠብቃቸው ዝር አላሉም … እንዲያውም ቤቴ መምጣት እርም ብለው ቀሩ … ወደ ሚሰሩበት ምግብ ቤት ሄጄ፣ ዘበኛውን ውዴን እና የሺ እንዲጠራልኝ ስጠይቀው፣ ቤቱን መልቀቃቸውን በደፈናው ነገረኝ … ቀና ስል ጤናዬ በረንዳው ላይ ቆማ ቁልቁል ስታየኝ፣ በርግጌ እብስ አልኩ፡፡
የት ሄዱ? እንደ እንፋሎት አየር ላይ በነኑ-ተነኑ…
የዚያኑ ዕለት ማምሻውን ጤናዬ አይኗን በጨው አጥባ ቤቴ መጣች፡፡ ሰይጣን ቤቱ እንደገባ ቆሌዬ ተገፈፈ…” አለና አረቄውን ሳበ፡፡ ለሻከረው ድምጹ ጥራት ይሆን? … እኔም አፕሬቲቬን ተጎነጨሁ - ለጆሮ ጥራት መሆኑ ነው፡፡
“ጤናዬም እየተንተፋተፈች … የምግብ ቤቱ ባለቤት የእነውዴን ነፍሰጡርነት ተጠራጥረው እንደጠየቋቸው… ሁለቱም ማመናቸውን … አስወርዳለሁ ብለው ሕይወታቸውን እንዳያጡ - ወደ ቤተሰብም ሂደው እንዲወልዱ አሳምነው፣ ሁሉንም አሟልተው እንደሸኟቸው መሰሪዋ ጤናዬ ነገረችኝ …
እነ ውዴ ሀገር ቤት በገቡ በመንፈቁ አንድ ዘመዴ ከአባቴ የተላከ ደብዳቤ ይዞልኝ መጣ። የሰማውንም ጉድ እንደ ዶፍ አወረደው፡፡ የአቶ አርጋው ልጅ ፍቃዱ፤ ሁለት የዋህ ልጃገረዶችን መስተፋቅር አስነክቶ ድንግልናቸውን ገሰሰ፤ አስረገዘ የሚለው ወሬ እንደ ተስቦ በአንዴ መንደሩን ማዳረሱን … በቅርቡ ከአዲስ አበባ የመጣ እማኝም፣ ጤናዬ ከፍቃዱ ቤት በምሽት ስትወጣ በአይኑ በብረቱ ማየቱን - ሦስተኛዋ እርጉዝ በቅርቡ ካልገባች ከምላሴ ፀጉሩ ይነቀል ብሎ ማውራቱን… ሀገር ጉድ አለ፡፡ ፍቃዱ አርጋው ከዚህ መንደር የወጣ ሳይሆን ነፍሱ ከሲኦል የወጣች፣ ደም የጠማኝ ጋኔንነቴ ፀድቆ “ሉሲፈር” የሚል ቅጽል እንደወጣልኝ … ዘከዘከልኝ።
የአባዬን ደብዳቤ አነበብኩት … በተከበረበት ሀገር በውርደት ቅስሙ መሰበሩን - የልጅ እባብን ማሳደጉን … ቢሞት ቀብሩ ላይ እንዳልደርስ … ያኔ ውስጤ ተናደ፤ ከቀምቃሚነቴ ጋር ተዳምሮ ለሞራል ውድቀት፣ ለብኩንነት በቃሁ-ወፈፍ አደረገኝ… ሥራዬም ተበለሻሸ … አመታት እንደ ወንዝ ፈሰሱ - ከብርሌ አጣቢነት የሕይወት ደለል ላይ ጣሉኝ…           

Published in ልብ-ወለድ

           በኢትዮጵያ ከ10-15% የሚሆኑ ጥንዶች ልጅ መውለድ እንዳልቻሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቢችሉ ወደህክምናው ከዚያም ባለፈ ወደየእምነታቸው በማዘንበል የሚያምኑትን መለመናቸው አይቀርም፡፡ ጠበብት ይህንን ችግር ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት ሳይንሳዊ ውጤቶችን ለህዝብ በማቅረብ አገልግሎት ላይ እያዋሉ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ IVF ነው፡፡ ዶ/ር እስክንድር ከበደ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ኮሌጅ የማህጸን እና ጽንስ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ስለ In Vitro Fertilization ለተጠየቁት ጥያቄዎች እንደሚከተለው መልስ ሰጥተዋል፡፡
ጥ/    የIVF  ህክምና በምን መንገድ የሚሰጥ ነው?
መ/    IVF ህክምና እርግዝናን ከማህጸን ውጭ በላቦራቶሪ ውስጥ እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው፡፡ አሰራሩም የሴትየዋን እንቁላልና የሰውየውን የዘር ፍሬ በመውሰድ እና በማዳቀል በቲዩብ ውስጥ በማዋሀድ እርግዝናው እንዲፈጠር የሚያስችል  ሳይንሳዊ ሕክምና ነው፡፡ የቆይታ ጊዜው እንደላቦራቶሪው የሚለያይ ሲሆን የማዳቀል ስራው ከተሰራ ሶስተኛ ቀን እስከ አምስተኛው ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ስለሚዋሀድ ወደ ሴትየዋ ማህጸን ገብቶ እድገቱን እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡  
ጥ/    የIVF ሕክምና ለእነማን ያስፈልጋል?
መ/    IVF ህክምና የሚሰጠው፡-
የማህጸን ቱቦ በተለያየ ምክንያት ለተዘጋባቸው ሴቶች፣
እንቁላል ከአቃፊዋ ወጥታ ከወንድ የዘር ፍሬ ተገናኝታ ወደ ማህጸን የምትገባው በቱቦው አማካኝነት ሲሆን ቱቦው በተለያየ ችግር ምክንያት ከተዘጋ እርግዝና እንዳይፈጠር ያደርጋል፡፡
እንቁላልን የሚያመነጨው ክፍል በስነስርአት እንቁላልን ያለማመንጨት፣
የሚወጣው እንቁላል ቁጥር እየቀነሰ መሔድና ጥራቱም በዚያው ልክ መቀነስ ካሳየ፣
የሴት ማህጸን ምንም እንቁላል የማያመርት ከሆነ፣
በተለያዩ ምክንያቶች የወንድ የዘር ፍሬ ቁጥር በጣም አናሳ ከሆነ... ወዘተ ናቸው፡፡
ጥ/    የሴትየዋ ማህጸን ምንም እንቁላል የማያመርት ከሆነ እንቁላል ከየት መጥቶ ይዳቀላል?
መ/    ሴትየዋ ማህጸንዋ እንቁላል የማያመነጭ ከሆነ የሚወሰደው እርምጃ ተመሳሳይ ሴት መፈለግ ነው፡፡ ከሴትየዋ ዘመዶች ወይንም አቅራቢያ ካሉ ሰዎች ወይንም ከሌላ ጋ በባህርይ በመልክ እና በተለያዩ ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች በተቻለ መጠን የምትመስል ሴት ተፈልጋ እንቁላልዋ ይወሰዳል፡፡ ከዚያም ከዚያች እንቁላል ማምረት ከማትችለው ሴት ባል የዘር ፍሬ ጋር ተቀላቅሎ በላቦራቶሪ ውስጥ ከተዋሀደ በሁዋላ ማርገዝ ወደማትችለው ሴት ማህጸን እንዲገባ ተደርጎ ልጅ እንዲወልዱ ይደረጋል፡፡ ስለዚህም IVF ሊሰራላቸው የሚገባቸው ሰዎች እንደዚህ ያለ እርግዝናን የሚከለክል ከባድ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡
ጥ/     ማህጸን ጽንስ አይቋጥርም ሲባል ምን ማለት ነው?
መ/    በመጀመሪያ ልጅ አለመውለድ ወይንም ኢንፈርቲሊቲ የሚባለውን ስንመለከት አንዲት   ሴትና ወንድ ለአንድ አመት ያህል አብረው እየኖሩ    እርግዝና ካልተፈጠረ ልጅ መውለድ አለመቻል የሚለውን ያመለክታል፡፡ ከዚህ ጊዜ ቆይታ በሁዋላ ሁኔታው ለምን እንደተከሰተ ለማወቅ ሲባል የህክምና ምርመራ ይደረጋል፡፡
ጥ/    ማርገዝ መቻልንና አለመቻልን ለማወቅ አንድ አመት ያህል መቆየት ግድ ነውን?
መ/    በእርግጥ ውሳኔው በእድሜ ደረጃ ተለያይቶ የሚሰጥ ነው፡፡ ለምሳሌ እድሜያቸው ከ30/አመት በታች የሆናቸው ሴቶች ማርገዝ አለማርገዛቸውን ለማወቅ አንድ አመት ያህል  መቆየት አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን እድሜያቸው ከ35/አመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ማርገዝ አልቻልንም ብለው ወደሕክምና ሊመጡ የሚገባቸው በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱም እድሜያቸው ከፍ እያለ ስለሆነ እና እርግዝናውን እስኪመጣ ሊታገሱበት የሚችሉበት ብዙ ጊዜ ስለማይኖራቸው ቶሎ ሕክምናውን እንዲያገኙ ለማድረግ ነው፡፡
ጥ/    እርግዝናን በሚመለከት የተፈጥሮ ህግ ምን ይመስላል?
መ/    የተፈጥሮውን ህግ ስንመለከት አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት አብረው መኖር በጀመሩ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ20-25% የሚሆኑት ሴቶች ያረግዛሉ፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት አንድ አመት ያህል አብረው ከሚኖሩ ሰዎች ውስጥ ከ80-90% ያህሉ ሴቶች ብቻ ያረግዛሉ፡፡ ስለዚህም ከዚህ በላይ እርግዝናው ይከሰት ይሆናል ብሎ መቆየቱ አስፈላጊ ስላልሆነ እንደእድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ አንድ አመት ድረስ ሳያረግዙ ቆይታ ካደረጉ በሁዋላ እርግዝናው ካልተከሰተ ሕክምናው እንዲጀመር ግድ ይላል፡፡
ጥ/    አንዲት ሴትና አንድ ወንድ እንደተገናኙ የማይረገዝበት ምክንያት ምንድነው?
መ/    አንዳንድ ጊዜ የጊዜ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት እንቁላልዋ የምትወጣው በወር አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ከተፈለፈለች በሁዋላ ቆይታዋ ለ24/ሰአት ያህል ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኩዋን የወንድ ዘር በየጊዜው የሚፈጠር ቢሆንም ጽንስ ለማፍራት ግን የወንድ የዘር ፍሬ የሴቷን እንቁላል ማግኘት ግድ ይሆንበታል፡፡ ስለዚህም የሴትዋ እንቁላል ከመውጣትዋ በፊት 12/ሰአት ከወጣች በሁዋላም እስከ 48 ሰአት ድረስ ባለው ጊዜ ወንድና ሴት ካልተገናኙ ጽንስ አይፈጠርም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ምንም እንኩዋን በትክክለኛው ጊዜ ግንኙነት ቢያደርጉም በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም ከጤንነት፣ ከተፈጥሮ ሁኔታዎች፣ ከአኑዋኑዋር ባህርይ ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ እርግዝናው ላይከሰት የሚችልባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡
ጥ/    በሕክምናው ዘርፍ ምን ይመከራል?
መ/    በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጥ የምክር አገልግሎት አለ፡፡ ለምሳሌ.. አንድ ባልና ሚስት በስራ ወይንም በተለያዩ ምክንያቶች አብረው የማይኖሩ ከሆነ እና በሚኖራቸው የተዛባ ግንኙነት ምክንያት እርግዝና ባይከሰት ልጅ ያለመውለድ ችግር አለ ተብሎ ሊደመደም አይችልም፡፡ ስለዚህ የሚቻል ከሆነ ባልና ሚስቱ አብረው መኖር አለባቸው፡፡ ያ ካልሆነ ደግሞ እንደባለሙያዎች ምክር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ ድረስ ግንኙነት ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እርግዝና ሊከሰት አይችልም፡፡  
ጥ/    እርግዝና እንዳይከሰት የወንድና የሴት ድርሻ ምን ያህል ነው?
መ/    26% የሚሆነው እርግዝና የማይከሰተው በወንድ ምክንያት ሲሆን በሴት ምክንያት ደግሞ ወደ 37% ይሆናል፡፡ በሁለቱም ምክንያት ወደ 30% ሲሆን እንዲሁም ምንም ምክንያት ሊገለጽለት በማይችል ሁኔታ ወደ 28% የሚሆነው ለእርግዝና አለመከሰት ምክንያት ነው፡፡ በህክምናው ዘርፍ የሚሰጡ የተለያዩ ሕክምናዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ... እንቁላል ቶሎ ቶሎ እንዲወጣ የሚያደርግ መድሐኒት አለ፡፡ እንዲሁም ለወንዶችም የሚሰጥ መድሀኒት አለ፡፡ ሁለቱም ተሞክረው የማርገዝ ሁኔታው ሊሳካ ካልቻለ የመጨረሻው እርምጃ IVF የሚባለው ሕክምና ነው፡፡
ጥ/       IVF ሕክምናው በአለም እውን ከሆነ ምን ያህል ጊዜ ሆነው?
መ/    IVF ሕክምና በአለም ላይ ወደ 20 አመት የሆነው ሲሆን በአሁኑ ጊዜም በብዙ ሀገራት የህክምና ማእከላቱ ተቋቁመው መውለድ ለማይችሉ ጥንዶች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህም ያለንበት ወቅት ተስፋን የሚያጨልም ሳይሆን ብዙዎች በዚህ ዘዴ ልጅ እያገኙ በመሆኑ የሚወለዱት ልጆችም ቁጥር ወደ በርካታ ሚሊዮኖች ደርሶአል፡፡
ጥ/    በላቦራቶሪ የሚፈጠሩ ልጆች እና በማህጸን የሚፈጠሩ ልጆች የጤንነት ወይንም ተፈጥሮአዊ ልዩነት አይኖራቸውም?
መ/    ምንም አይነት ልዩነት የላቸውም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በላቦራቶሪ የሚፈጠሩት ልጆች በቲዩብ ውስጥ ቆይታ የሚያደርጉት ውህደቱ እስኪፈጠር ድረስ ከአምስት ቀን ያልበለጠ ጊዜ ነው፡፡ በማህጸን የሚፈጠረውም ቢሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ከውህደት ያለፈ ምንም ተግባር የለውም። የሴትየዋ እንቁላል መቼ እንደምትወጣ ታውቆ ሁኔታውን ምቹ የሚያደርጉ የህክምና ሂደቶች ከተጠናቀቁ በሁዋላ ልክ እንቁላልዋ ስትወጣ ተወስዳ የወንድየው የዘር ፍሬም እንዲሁ ተወስዶ በቲዩብ እንዲቀላቀሉ ከመደረጉ በስተቀር ሂደቱ በማህጸን ውስጥ ያለው አይት ነው፡፡ ስለዚህም የዘር አፈጣጠሩ ያው ከእናት እና አባቱ ስለሆነ ያንኑ ጠብቆ ይወለዳል፡፡
ጥ/    IVF ሕክምናው በኢትዮጵያ ይሰጣል?
መ/    IVF ሕክምናው በኢትዮጵያ አይሰጥም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ሀገራት በመሰጠት ላይ ሲሆን በቅርባችን በሱዳን ካርቱም 11/የሚሆኑ ማእከላት አገልግሎቱን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ ሕክምናው የሚሰጥ ሲሆን በህንድ አገር ግን በስፋት የሚሰጥ በመሆኑ ዋጋውም ከሌሎች አገሮች በተሻለ መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ በተረፈ በአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ኤሽያ ውስጥ ሕክምናው ይሰጣል፡፡ በኢትዮጵያ እስከአሁን ሕክምናው ካልተጀመረበት ምክንያቶች አንዱ ሕጉ መስተካከል ስላለበት ነው፡፡ መቼ እንደሚጸድቅ ባይታወቅም ጉዳዩ ግን ከፓርላማ መድረሱን ይነገራል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከ10-15% የሚሆኑ ባለትዳሮች ልጅ ያለመውለድ ችግር እንዳለባቸው የሚታወቅ ሲሆን ህጉ ጸድቆ ይፋ ከተደረገ ሕክምናው ይጀመራል የሚል ተስፋ አለ፡፡   

Published in ላንተና ላንቺ

      “አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በሕይወት ቢኖር ሙዚቃ የጀመረበትን 56ተኛ ዓመት ያከብር ነበር። እኔ ሙያው ላይ ከተሰማራሁ 52 ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ፡፡ ከሊስትሮ ሥራ ጀምሬ፣ በምግብ ቤት ውስጥ ተቀጥሬ ሰርቻለሁ፡፡ በአናፂነት ሙያ ላይ የተሰማራሁበት ጊዜ ነበር፡፡ በድምፃዊነትም በትምህርት ቤት፣ በጃንሜዳ፣ በሚካኤል፣ በጊዮርጊስና በሩፋኤል አብያተ ክርስቲያናት አገልግያለሁ፡፡ አሁንም በየመድረኩ በሙያዬ በመሥራት ላይ እገኛለሁ፡፡
“እኛ በቀዳሚነት መንገድ ጠርገን ተስፋ የሚጣልበት አሁን ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ዛሬ በርካታ ድምፃዊ፣ ግጥምና ዜማ ደራሲ፣ ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች … አሉ፡፡ ሙያውና ባለሙያው ተከብሯል፡፡ በቀድሞ ዘመን ‘አዝማሪን በቅራሬ ማባበል ነው’ በሚል በንቀት እንታይ ነበር፡፡ ሙያውን በተመለከተ በዚህ ዘመን ከሚታዩ ጉድለቶች ውስጥ እንደ ቀድሞ ዘመን መድረክ ሞልተው የሚታዩ ትላልቅ ኦርኬስትራዎች አለመኖራቸው አንዱ ነው፡፡
“ሙያውንና ባለሙያውን ማሳደግ ዓላማ ያደረገ የሙዚቀኞች ማህበር የማቋቋም ጥረት ማድረግ ከተጀመረ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ብዙ አፈናና ጫናም ነበረብን፡፡ ማህበር እንዲቋቋም ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ፣ ሻለቃ ጽጌ ፈለቀ … የመሳሰሉ ሰዎች ብዙ ደክመዋል፡፡ ለዚሁ ዓላማ በምድር ጦር፣ በፖሊስ ሠራዊት፣ በሀገር ፍቅር፣ በራስ ቴአትር … በነበሩ የሙዚቃ ክፍሎች የተደረገውም ድካም ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡
“የዚያ ጅማሬና ጥረት ውጤት ሆኖ አሁን በአዲስ መልክ ተቋቁሞ መሥራት የጀመረው የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ትልቅ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አያለሁ፡፡ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያዎች ከየት እንደተነሳን፤ ምን መልካም ዕድልና ችግር እንደገጠመን፤ በሙያው ውስጥ እነማን እንደነበሩ፤ አሁን ቅርስ ሆነው የሚገኙት የሙዚቃ ሥራዎችን ለማቀናበር የተከፈለው ድካም ምን ይመስል እንደነበር … ለማስተዋወቅ ማህበሩ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ ተተኪዎችንም ለማፍራት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ዛሬ ያስመረቃቸው ወጣቶች ያቀረቧቸው ሥራዎች ምስክር ናቸው። የተስፋ ብርሃን እየታየ ነው፡፡ ተስፋው ቀጣይ እንዲሆን እንተባበር፡፡”
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ከሰላም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት “የአርባን አዲስ ፕሮጀክት የአንድ ዓመት ወርክሾፕ ስልጠና” ተከታትለው ያጠናቀቁ 30 ሰልጣኞችን ለማስመረቅ የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ በተሰናዳው ፕሮግራም የተጋበዘው አርቲስት ማህሙድ አህመድ ነበር ከላይ የቀረበውን ንግግር ያደረገው፡፡
አዘጋጆቹ በጠበቁት መጠን ብዙ ሰው ባይመጣም ሥራ፣ ሥምና ታዋቂነታቸው ከፍ ብሎ የሚታይ ታላላቅ እንግዶች ግን ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ፣  ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ፣ አርቲስት መርዓዊ ስጦት፣ ጋሽ ተስፋዬ አበበ፣ አርቲስት ሃይማኖት ዓለሙ … የመሳሰሉ እንግዶች በተገኙበት የዕለቱ የክብር እንግዳ ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋም ንግግር አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር የሙዚቃ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶችን አሰልጥኖ የሙያ ሰው ለማድረግ ያሳየው ጥረት የሚደነቅ ነው ያለው ግርማ ይፍራሸዋ፤ “ይህ ጥረት የአገራችንን ሥነ ጥበብ ያሳድጋል፤ ጥበብ የሚያልቅ ስለሆነ ወጣቶች ዕውቀታቸውን በትምህርትና ስልጠና ለማሳደግ መጣር ይኖርባቸዋል፡፡ የጥበብ ጥማታችሁን ለማርካት ዕውቀት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ማህበሩ የጀመረው እንዲህ ዓይነት ተግባር ከግቡ እንዲደርስ እኔም አቅሜ የፈቀደውን ለመርዳት ፈቃደኛ ነኝ” ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ዳዊት ይፍሩ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር የአመሠራረት ታሪኩ ረጅም መሆኑንና በቅብብል ለዛሬ መድረሱን አመልክተው፣ የነበረባቸው የቢሮ ችግር አሁን መቀረፉን ገልፀዋል። የሙዚቃ ሙያና ባለሙያ አገርና ሕዝብን እያገለገሉ ብዙ ዘመናትን አስቆጥረዋል ያሉት አርቲስት ዳዊት ይፍሩ፤ ማህበራቸው የሙዚቀኞችን ሥራና የሕይወት ታሪክ እንዲታወቅ ከማድረግ ባሻገር ተተኪ ወጣቶች ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
“የማህበርና የባለሙያዎችን ታሪክ በድረ ገፃችን በማስፈር ለሕዝብ አቅርበናል፡፡ ብዙ ታላላቅ ሥራዎችን ያከናወኑ አንጋፋ ባለሙያዎች በእርጅና ምክንያት መድረክ እያጡ ነው፡፡ እነሱን ለማገዝ የነደፍነው እቅድ አለ፡፡ ወጣቶቹ ከአንጋፋዎቹ እንዲማሩ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህንን ዓላማችንን በማገዝ ረገድ ሰላም ኢትዮጵያ ባለፉት 3 ዓመታት አብሮን እየሰራ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ዛሬ ያስመረቅናቸው 30 ወጣቶች በሙዚቃው ዓለም ሲሰማሩ ሙሉ የሚያደርጋቸውን የተለያየ ዕውቀት እንዲያገኙ አድርገናል ያሉት የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንቱ፤ ስለ ቅጂና ተዛማጅ መብቶች ምንነት፣ በሕገ ወጥ መንገድ ስለሚባዛው ካሴትና ሲዲ ስለ ስቱዲዮ ቴክኒክ፣ ስለ መሠረታዊ የኮምፒዩተር አጠቃቀም፣ ስለ ሙያ ሥነ ምግባር … ስልጠና እንደተሰጣቸው አመልክተዋል። ሰልጣኞቹም በዕለቱ የተለያዩ ታዋቂ ድምፃዋያንን ሥራዎች በማቅረብ የምረቃ ሥነ ስርዓቱን ከማድመቃቸውም ባሻገር የተማሩትንም በተግባር አሳይተዋል፡፡  

Published in ጥበብ

ከፍተኛ ተሰጥኦ እንዳላት የሚነገርላት የኢትዮጵያ ጃዝ አቀንቃኝ የሺ ደምመላሽ በሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ በኒውዮርክ የሙዚቃ ኮንሰርት እንደምታቀርብ ታዲያስ መፅሄት ዘግቧል፡፡
የጃኖ ባንድና የጂጂን ሥራዎች ያሳተመው የኒውዮርኩ ፕሮዱዩሰር ቢል ላስዌል “ፋኖ” የተሰኘ ዘፈኗን ዳግም አዋህዶ እያቀናበረላት ሲሆን የሺ አዲስ አልበም ከላስዌል ጋር የመስራት ዕቅድ እንዳላት ታውቋል፡፡
ድምፃዊቷ የኒውዮርክ ኮንሰርቷን የምታቀርበው ከ “ቅኔ” ባንድ ጋር ነው ተብሏል። በኢትዮጵያ አይዶል ዳኝነቷ የምትታወቀው የሺ፤ ከያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት በፍሉትና በተጓዳኝ በፒያኖ አጨዋወት ተመርቃለች፡፡ አርቲስቷ “ቅኔ” የተሰኘ የመጀመርያ አልበሟን የዛሬ ሁለት ዓመት ለጆሮ ማብቃቷ ይታወሳል፡፡   

Saturday, 08 March 2014 13:41

በቅኔ ፈጠራ ሚዛናዊ ሥራ

     ሰሞኑን “ቅኔያዊ የዕውቀት ፈጠራ” የሚል በቅኔ ሥራ ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ እጄ ላይ ገብቶ ከገበታ ገበታ አነበብኩት፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጅ አቶ ማርየ ይግዛው ሲሆኑ አሳታሚው ጎቴ ጀርመን የባህል ማዕከል ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ ብር 25 ነው፡፡ የታተመበት 2006 ዓ.ም እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
መጽሐፉ ለሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ እንዲሆን በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ ተመራማሪው አቶ ማርዬ ይግዛው በሥራው ብዙ የደከሙበትና የታከቱበት መሆኑን የምንረዳው መጽሐፉን አንብበን ስንጨርስ ነው፡፡ መጽሐፉ በይዘትም በቅርጽም የተስተካከለ፣ ተነባቢና ስለ ቅኔ ይትብሃል አብጠርጥሮ የሚናገር ማለፊያ ሥራ በመሆኑ፣ በታሪክ መረጃነት በእያንዳንዱ አንባቢ እጅ መቀመጥ ያለበት ሥራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
አቶ ማርዬ በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸውን ቅኔያት ያሰባሰቡት፣ በየቅኔ ቤቶቹ በመዘዋወርና በአካል ከየቅኔ መምህራኑና ዘራፊዎች ዘንድ በመገናኘት ነው፡፡ አቶ ማርየ ከጉባዔ ቃና አስከ ዕጣነ ሞገር ያለው የቅኔ ይትበሃል ምን እንደሆነ በአጉሊ መነጽር ያመለክቱናል። ከቅኔያቱ ልዩ ልዩ ባሕርያት ተነሥተን ፈጠራዎቹ ለምን ለምን ጥቅም እንደሚውሉ እንረዳለን፡፡
አቶ ማርየ ቅኔ ሁሉ ግጥም እንደሚሆን፣ ግን ግጥም ሁሉ ቅኔ እንደማይባል፤ ቅኔም በሰምና ወርቅ የተመሠጠረ ድርብ ትርጉም ያለው እምቅ ሥራ እንደሆነ ያሠምሩበታል፡፡ ይህም ቅኔንና ግጥምን ለሚያምታቱ ለዘመኑ ጸሐፍት ጥሩ ማስገንዘቢያ የሚሆን ነው፡፡
ለምሳሌ ነጠላ ትርጉም ያለውና የሚከተለው ተራ ግጥም ቅኔ እንደማይባል አቶ ማርየ በምሳሌ ያስገነዝቡናል፡፡
“ከዚህ አንስቶ እስከፎገራ፣
መኪና ቆሞ በቀኝ በግራ፣
ገድሎ ፎካሪ እዝብ ሲያወራ”
ገጽ 19 እና 20)
አንዳንድ የዘመናችን ጸሐፍት እንደዚህ ዓይነት ወሸከሬ ግጥም ከገጠሙ በኋላ ራሳቸውን “ባለቅኔ እገሌ” ብለው ያንቆለጳጵሳሉ፡፡ በመሠረቱ ግን አቶ ማርዬ እንዳሉት፤ እንደዚህ ያለው ግጥም ሰምና ወርቅ የሌለው፣ ነጠላ ትርጉም  ያለው ተራ ግጥም ነው፡፡ ቅኔ በሰምና ወርቅ ባይነገር ኖሮ ከእንደዚህ ያለ ግጥምነት ያልዘለለ ስለሚሆን አሁን የያዘውን ጣዕም አያገኝም ነበር፡፡ ቅኔም አይባልም ነበር፡፡
ተመራማሪው እንደሚሉት፤ ትንሽ ተሰጥኦ ያለው ያልተማረ ሰው እንኳን ግጥም እንደሚገጥም ይታወቃል፡፡ ቅኔ ግን አንድን ጥልቅ ሐሳብ በሌላ ሐሳብ ሸፍኖ በሰምና ወርቅ ዓይነት መቅረቡ ልዩ ያደርገዋል። በሰም የተሸፈነውን ምሥጢር /ወርቅ/ ተመራምሮ ማግኘቱ በራሱ ቅኔን ሁልጊዜ በጉጉት እንዲጠበቅ የሚያደርገው ሲሆን ከምግብና መጠጥ ይልቅ ልዩ እርካታን እንደሚሰጥም ግልጽ ነው፡፡
ሌላው ሁሉ ቀርቶ የቅኔ ግጥም በዜማ የሚዜም በመሆኑ መጠኑ ላይ ማንም ምንም መጨመር ወይንም መቀነስ አይችልም፡፡ የተለያዩ የቅኔ ዓይነቶች ሁሉ የየራሳቸው መጠን አላቸው፡፡ መጠኑ የሚወሰነው በየቅኔዎች ባሉት ስንኞች ብዛት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ስንኝ ባለው የቃላት መጠን ጭምር ነው፡፡
በዚህ ዓይነት አንድ ግጥም በሰምና ወርቅ መንገድ ቢቀርብም የቅኔ፣ የዜማ ልክ ከሌለው  (በአንዱም የቅኔ ዓይነት ግጥሙን አስገብቶ መዘመር ካልተቻለ) ቅኔ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ የዘመናችን የአማርኛና የሌላ ቋንቋ ገጣሚዎች ይህንን ልኬት በአግባቡ መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡    
አቶ ማርየ እንደጠቀሱት፤ መልአከ ሕይወት ፍሬስብሐት የተባሉ ባለቅኔ በኤድስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስብሰባ ላይ ያቀረቡትን የራሳቸውን ሰምና ወርቅ አዘል ግጥም ድርሰት አሉት እንጂ ቅኔ አላሉትም።
“እናንተ ወጣቶች ቀን አለ መስሏችሁ፣
ከገጠሩ ኑሮ ከተማ ገብታችሁ፣
መሠረት የሌላት ጎጆ መሥርታችሁ፣
ዘማለች አደራ እንዳትወድቅባችሁ፡፡”
ግጥሙ ከአንድም ሁለት ወርቅ አለው፡፡ ዘማለች (ዘማ፣ ሴተኛ አዳሪ፣ ሸርሙጣ፣ ማለት ነው) እና እንዳትወድቅባችሁ፤ እናንተ ከሴቲቱ እግር ስትወድቁ የኤድስ በሽታ ከእናንተ ላይ እንዳትወድቅባችሁ) የሚለው ራሳቸው ደራሲው ድርሰት አሉት እንጂ ቅኔ አላሉትም፡፡ ምነው ቢሉ ቅኔ ከድርሰትም ከግጥምም የላቀ ባሕርይ ስለአለው ነው፡፡
በብዛት የምናገኛቸው ቅኔዎች በግእዝ ቋንቋ የተደረሱ ናቸው፡፡ ማንኛውም ተማሪ ቅኔ ቤት ሲገባ መጀመሪያ የሚያጠናውም የግእዝን ቋንቋ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሌላው ግጥም በየቋንቋው የሚቀርብ ሲሆን ቅኔ ግን በግእዝ ቋንቋ ላይ የተገደበ ነው። የሰምና ወርቅ ባህል የተለመደውም በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡
አጥኚው እንደተነተኑት እንደ ግእዝ ቋንቋ በቅኔ የሠለጠነ የለም እንጂ ቅኔ የአንድ ቋንቋ ብቻ ጥገኛ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ መለኪያዎች ተቀርጸውለት፣ ሥርዓት ተበጅቶለት ትምህርት ላይ የዋለው ግን የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡ የእርሱን መለኪያ ተከትሎ (መጠን ሰም ወርቅ) አሳክቶ በሌሎች ቋንቋዎችም መቀኘት ይቻላል። ለምሳሌ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በእንግሊዝኛ …፡፡ ከጎንደር ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የግእዝ ብቻ ሳይሆን የአማርኛ ቅኔ ወይም ግእዝንና አማርኛን በማቀላቀል ጉራማይሌ ወይንም ፍርንዱስ ቅኔ ማቅረብ እየተለመደ መምጣቱን አቶ ማርየ ጠቅሰው፤ የተለያዩ መወድስ ቅኔዎችን ለማስረጃነት አቅርበውልናል፡፡  ለዚህም “ካህነ ቀላዋጭ ኢትናቅ ምጥዋ ነጋዴ” የሚለው የቆየ መወድስ፤ ቅኔ አብነት እንደሆነ ያነሡት ሲሆን ሙሉ በሙሉ በአማርኛ የቀረበ መወድስም ያስነብቡናል፡፡ ቅኔው የሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሺፈራው ዘጨጎዴ ሐና ነው፡፡
ከነ ቅዱስ ያሬድ ሆቴል ገብተው የሚጠጡ ጣዕም ያለውን ቢራ ምሥጢር በየሰዓቱ በየሰዓቱ፡፡
ሊቃውንተ ጎጃም ያሬድ የሚያስከብራቸው በእውቀቱ፡፡
ከኢትዮጵያ እስከ አሜሪካ አያልቅም ቢቀዳ ቢቀዳ መወድስ ድራፍቱ፡፡
የሚቀርብ ለሁል ጊዜ በነ ቅዱስ ያሬድ ሆቴል እየተዘጋጀ ከሊቃውንቱ፡፡
ምሥጢር ጣዕም ያለው ቢራ ሁሉን የሚያስደስት ጥራቱ፡፡
ቀረበኒ ለእያንዳንዱ ለእያንዳንዱ በፊት በፊቱ፡፡
እንዲቀርብ አሁን አዘዋልና በቤቱ፡፡
ጉባኤ ቃና መወድስ ክቡራን መኳንንቱ፡፡
ይህ ቅኔ በሰምና ወርቅ የተጌጠ ነው፡፡ የሰምና የወርቅ ትርጉሙም በሚገባ ተብራርቶ ቀርቧል፡፡ ግእዝ ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛ ጭምር የተቀየጡ ጉራማይሌ ቅኔዎችንም ማግኘት ይቻላል፡፡
የሚከተለው እንግሊዝኛ፣ ግእዝና አማርኛ ጉራማይሌ መወድስ የመሪጌታ ይቻለዋል ጎሽሜ ነው። ገጽ (25-26)
መወድስ
ኦ ብራዘርስ ውሉደ ጥምቀት
እንተ በጉባኤ ንትጋባእ ውስተ ታዕካ ዘቅድስና፣
ሮር ዘሴክ ኦፍ ሳይንቲፊክ
ኢንተረስት ውሉድ ዘጥዑም መና፡፡
ወይነ ምስጋና ዘመላእክት
ውስቴታ ተቀድሃ ከመ ከመ ያስተፍስሕ የሰው ልቡና።
ኸርትሂ የገበሬ እርሻ እንዳያገኛት ሙስና፡፡
ይዝነም ቃለ ወንጌል በፍቅር ወበትሕትና፡፡
እስመ ዝናመ ጽድቅ ተርዕየ በዘ ጳውሎስ ደመና።
ወደቂቀ ጳውሎስ አእዋም አህመልመሉ ጠለ ሲና፡፡
ይህ ቅኔ ትርጉምም ምሥጢርም ያለው ሲሆን በመጽሐፉ በሚገባ ተብራርቷል፡፡ መጽሐፉን ማንበብ ይጠቅማል፡፡ በኦሮምኛ የተዘጋጁ ቅኔዎችም አሉ፡፡ አቶ ማርየ ይግዛው ይህንን የቅኔ ምርምር ሥራ ሠርተው፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመቀበያ ሰዓታቸው ሞት ቢቀድማቸውም የሠሩት ሥራ ሕያው ምሥክር ሆኖ ለዘለዓለም ስለሚኖር እንደሞቱ አያስቆጥርም፡፡ ይህን ዋጋ ያለውን ሥራ ባለቤታቸውና ወ/ሮ ፍቅርና የጀርመን ባህል ማዕከል ለኅትመት በማብቃታቸው፣ አቶ ዮናስ ታረ    ቀኝም በመተባበራቸው በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
አቶ ማርየ በየቅኔ ቤቶች እየተዘዋወሩ ከቅኔ መምህራና ዘራፊዎች ከአገኙት የቅኔ ዕውቀት በመነሣት ስለቅኔ ምንነትና ባሕርያት፣ ስለቅኔና ግጥም፣ ስለቅኔ ምንጭና አጀማመር፣ ስለ ቅኔ ባህል (ነጠቃ ዘረፉ፣ ግልበጣ)፣ ምስጠት፣ቅኔ እንዴት ለምርምር፣ ለፍልስፍናና ለሥነምግባር ማነጫነት እንደሚያገለግል፤ በሀገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ስለአለው ሚና…በምሳሌነት የቅኔ ዘለላዎችን እየመዘዙ ያመለክቱናል፡፡ ችግርን፣ ፈተናን በቅኔ አማካኝነት ማስረዳትም ሌላው የቅኔ ባሕርይ መሆኑን ከመጽሐፋቸው እንረዳለን፡፡ አስካል ቸኮል፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለግብር ተጠርተው ሲሄዱ ባለሟል አያውቃቸው ኖሮ፣ ከአዳራሹ ውጪ ሜዳ ላይ ተቀምጠው እንዲስተናገዱ ቦታ ያመቻችላቸዋል፡፡ በዚህ ያልተደሰቱት ባለ ቅኔ፤ በቁማቸው የሚከተለውን አማርኛ ግጥም በመናገራቸው ምክንያት ሁኔታው ተሰምቶ ወደ አዳራሽ እንዲገቡ ተደርጎ በክብር ተስተናግደዋል፡፡
ግጥማቸው
“እንክርዳድ ተለቅሞ ለግብር ሲደርስ፣
አስካል ጥሩ ስንዴ በሜዳው ፍስስ፡፡” የሚል ነው። ዝነኛው ባለቅኔ ሌሎችን እንደ እንክርዳድ ራሳቸውን ደግሞ እንደተፈተገ ስንዴ ቆጥረዋል፡፡  
አቶ ማርየ 85 ያህል ቅኔዎችን አሰባስበው የተነተኗቸው በቃለ መጠይቅ መልክ መምህራንንና የቅኔ ተማሪዎችን በማነጋገር ነው፡፡ ባለ ቅኔዎቹ ለማርየ ጭምር ቅኔ ዘርፈውላቸዋል፡፡ በተረፈ በዚህ ሥራቸው ውስጥ በገፅ 182 ላይ ዕጣነሞገር የተባለው (በስሕተት) እዝል ክብር ይዕቲ ሲሆን በገፅ 146 ላይ በቀረበው ጉባኤ ቀና
“እታገኝ ደመርኪ እምላእለ ክብርኪ ክብር፡፡
ለነዳይ እስኪት እስመ ወህበኪ ቂንጥር” የተባለው በስሕተት ሲሆን መነሻውና መድረሻው ሳድስ ሳይሆን ግዕዝ ነውና ረ ፡፡ ክብረ፡፡ ቂንጥረ ነው፡፡

Published in ጥበብ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ት/ቤት የ50ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓሉን አስመልክቶ ብሔራዊ የምስለ ችሎት ውድድር እንደሚያካሂድ ገለፀ፡፡ ከመጋቢት 16-18 የሚካሄደው ውድድር፤ በአለም አቀፍ ወንዞች አጠቃቀም ዙሪያ የተዘጋጀ ሲሆን በአገሪቱ ያሉ የሕግ ት/ቤቶች በሙሉ ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡ የመጨረሻ የዋንጫ ውድድር መጋቢት 18 ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት የሚከናወን ሲሆን በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ምርምር ያደረጉ ምሁር በአገራችን ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አስመልክቶ ስለሚነሱ የህግ ክርክሮች የማጠቃለያ ንግግር እንደሚያደርጉ የህግ ት/ቤቱ ጠቁሟል፡፡

         የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 22ኛውን አመታዊ ጉባኤውን እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር February 24-25 በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል አካሂዶአል፡፡ ጉባኤው በተካሄደበት ወቅት የማህበሩ አባላት እና ተባባሪ አባላት የተገኙ ሲሆን የተለያዩ ድርጅቶች ተወካዮችም ተሳትፈዋል፡፡ ኮንፍረንሱን የከፈቱት ዶ/ር ታዬ ቶሌራ ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚኒስትር ደኤታው ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡  
የማህበሩ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት ማህበሩን ወክለው ባቀረቡት የመግቢያ ንግግር
“ ...ለ22ኛው አመታዊ ኮንፍረንስ እንኩዋን ደህና መጣችሁ እያልኩ በመቀጠል ያለኝን የልብ ሀዘን ለመግለጽ እድሉን ልጠቀም እወዳለሁ፡፡ ዶ/ር አየለ ኃይሉ በምስራቁ የአገራችን ክፍል የነበረንን ቅርንጫፍ ቢሮ ይመሩ የነበሩ ...በአካባቢው ላሉ እናቶችና ህጻናት የተሟላ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን በድንገትና በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወታቸው በማለፍዋ ሐዘናችን ከልብ የመነጨ ነበር፡፡ ከመካከላችን በሞት የተለዩንን የማህበራችን አባል የሆኑትን ዶ/ር አየለ ኃይሉን ለአንድ ደቂቃ በህሊናችን እናስባቸው ዘንድ የኮንፍረንሱን ተሳታፊዎች እጠይቃለሁ...” በማለት የህሊና ጸሎት ተደርጎአል፡፡
በመቀጠልም ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት ባቀረቡት የመግቢያ ንግግር እንደገለጹት ባለፈው አመት ESOG ከተለያዩ አጋዥ ድርጅቶች እና አብረው ከሚሰሩ አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የእናቶችን ጤና ለማሻሻል በርካታ ጥረቶችን አድርጎአል፡፡ ከሚጠቀሱት መካከልም በወሊድ ጊዜ የሚከሰት የደም መፍሰስ እና በእርግዝና ጊዜ የሚከሰትን የደም ግፊት ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የበኩሉን ጥረት አድርጎአል፡፡ እነዚህን በተለይም ሴቶችን በእርግአዝና እና በወሊድ ጊዜ ለአደጋ የሚያጋልጡ ሕመሞችን በሚመለከት ለባለሙያዎች በመከላከል ላይ ያተኮረ አውደጥናት በተከታታይ ተሰጥቶአል፡፡ በዚህም ተሳታፊዎች ችግሩን እንዴት ማቃለል እንደሚገባ አምነው ለመከላከሉ የራሳቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ 52/ ከሚሆኑ የግል የህክምና ተቋማት ጋር በተለያዩ መስተዳድር አካላት ጋር ...አዲስ አበባን ጨምሮ ይሰራል፡፡ በዚህም ፕሮግራም ከ/100,000/ በላይ እናቶች የእርግዝና ክትትል ያደረጉ ሲሆን ከ/2207/ በላይ የሚሆኑ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ እናቶች እና ልጆቻቸው ከፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይህንን ፕሮግራም ከኢሶግ ጋር በመሆን የሚሰሩ የግል የህክምና ተቋማት በአሁኑ ወቅትም Option B+  የተባለውን ፕሮግራም ...ማለትም እርጉዝ ሴቶች በምርመራ ወቅት ቫይረሱ በደማቸው ከተገኘ ወዲያውን የህክምና እርዳታውን እንዲያገኙ የሚለውን አሰራር በመከተል አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት በኦክቶበር 2013/ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የመጀመሪያውን የAFOG&FIGOን ስብሰባ በኢትዮጵያ /አዲስ አበባ/ ማካሄዱን ገልጸው በዚህም ስብሰባ ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ወደ /807/ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኮንፍረንሱ ከተለያዩ ሐገራት የመጡ ባለሙያዎች አስተሳሰባቸውን የተጋሩበት እና በተለይም በምእተ አመቱ የልማት ግብ ከሚጠበቁት ውጤቶች አንጻር ሁኔታዎች የሚሻሻሉበትን መንገድ መወያየት የተቻለበት ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ወደ /300/ የሚደርሱ ሳይንሳዊ ወረቀቶች እና ፖስተሮች ቀርበው እንደነበር የማይዘነጋ ነው ብለዋል፡፡
22ኛው የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ኮንፍረንስ ለዚህ አመት መነጋገሪያ እና የትኩረት ወይም የስራ አቅጣጫ ያደረገው መረጃን መሰረት ያደረገ የእናቶች እና የህጻናት ጤን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምእተ አመቱን የልማት ግብ ቁጥር 4/ን አሳክታለች፡፡ የእናቶችን ጤንነት ማሻሻል እና ሞትን መቀነስን በሚመለከትም ስራዎች ለመሰራታቸው አመላካች ነገሮች ይታያሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ችግሮች እንዲቃለሉ የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት ማህበሩ እና አባላቱ በተለመደው መንገድ ጥረታቸውን ይቀጥላሉ እንደ ዶ/ር ይርጉ ንግግር፡፡
አመታዊው እና የማህበሩ የትኩረት አቅጣጫ መረጃ ላይ የተመሰረተ የእናቶችና የህጻናት ጤና ሲሆን በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ጥናታዊ ስራዎች ቀርበዋል፡፡
በስብሰባው ላይ ከቀረቡት ጥናታዊ ስራዎች መካከል ከእናቶች ወደህጻናት የኤችአይቪ ቫይረስ እንዳይተላለፍ በመቀነስ ዙሪያ ፕሮግራሙን እና ሳይንሳዊውን አተያይ የተመለከተ ይገኝበታል፡፡ እንዲሁም በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት፣ ጨቅላ ሕጻናትን፣ የእናቶች ሞትን ምክንያት ማወቅን፣ በአማራ ሁለት ወረዳዎች ላይ ያተኮረ የእናቶች እና የህጻናት ጤና ክትትል የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በደቡብ አካባቢ በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እና ተያይዞም በኤችአይቪ ኤይድስ ዙሪያ የሚደረገውን የጤና ክትትል እንዲሁም እናቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ በተለይም በመውለጃ ሰአት ሊደርስባቸው የሚችለውን የጤና ጉዳት አስቀድ መው ሊያውቁ እንደሚገባ የሚጠቁም ጥናት ከሐራማያ ቀርቦአል፡፡ ከላይ የተገለጹት በኮንፍረንሱ ላይ ከቀረቡት ጥናቶች በመጠኑ የተወሰዱ ናቸው፡፡
ስብሰባውን የከፈቱት ዶ/ር ታዬ ቶሌራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ...
“... በእናቶች እና ሕጻናት ጤና ላይ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ብዙ ለውጦችንም እያታዩ ነው፡፡ በተለይም ነብሰጡር እናቶች በእርግዝና ወቅት ክትትል እንዲያደርጉ እና በጤና ተቋም እንዲወልዱ የሚያስችላቸው አሰራር በስፋት ተዘርግቶ በዚህም አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ እናቶች ለመውለድ ሲመጡ አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ እየተደረገ ነው፡፡ ይህንንም ለማሟላት አስፈላጊው ስልጠና እና የህክምና መገልገያ አቅርቦቶች እየተሟሉ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህብረተሰቡን በሚመለከት የጤና የልማት ሰራዊት በየቦታው ተገንብቶአል፡፡ ይህ ሰራዊትም ሁሉም እናቶች በጤና ጣቢያ ሄደው እንዲወልዱ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ይህንን ፕሮግራም በጥንቃቄ እና በትኩረት እየተከታተሉ ያስፈጽማሉ፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ሰአት በጤና ተቋም የመውለድን ባህርይ አምና በተመሳሳይ ሰአት ከነበረው ሁኔታ ጋር ስናነጻጽረው በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ወደ 30% ያህል አድጎአል፡፡ ዶ/ር ታዬ አያይዘው እንደገለጹትም የተያዘው አሰራር በዚህ አካሄድ ከቀጠለ በአመቱ መጨረሻ ላይ 50% ወይንም 60% እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእናቶችን ጤና ከመጠበቅ እና ሞትን ከመቀነስ አንጻር ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ  የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ሲሆን የዚህም አላማው እናቶች በመረጡ ጊዜ ልጆችን እንዲወልዱ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን በሚመለከትም ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን የኤክስቴንሽን ሰራተኞች በየቀበሌው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የጤና የልማት ሰራዊቱም ይህንን እንደ አንድ ትልቅ ተልእኮ ወስዶ የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ የዚህ የስራ ውጤት እንደሚያሳየውም ቀደም ባሉት አመታት ወደ 27%  የነበረውን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽነት ወይንም ተጠቃሚነት ዛሬ ግን ወደ 39% ደርሶአል፡፡ ስለዚህም ጥሩ ለውጦች እየተመዘገቡ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው የጨቅላ ሕጻናት ጤንነት ጉዳይ ሲሆን አገልግሎቱም እየተስፋፋ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የህጻናት ሞት በመቀነሱ በምእተ አመቱ የልማት ግብ ስኬት ላይ ለመድረስ ተችሎአል፡፡ በአጠቃላም አሁን ያሉት እንቅስቃሴዎች እጅግ የሚያበረታቱ ቢሆንም ወደፊት ደግሞ ከተመዘገበው በላይ ውጤትን ለማምጣት ጠንክረን መስራት እንዳለብን እናምናለን ብለዋል ዶ/ር ታዬ ቶሌራ፡፡
የህክምና ባለሙያዎች በከተሞች ካልሆነ በስተቀር ህብረተሰቡ ዘንድ የመድረሳቸው ሁኔታ እምብዛም አይደለም በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ ዶ/ር ታዬ ቶሌራ ሲመልሱ...
“...በእርግጥ መስራት የሚገባንን ያህል ሰርተናል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን በእያንዳንዱ ጤና ጣቢያ ሁለት ሁለት አዋላጅ ነርሶችን አሰልጥነን መድበናል፡፡ በሆስፒታሎችም ከአዋላጅ ነርሶች በተጨማሪ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ተመድበው እየሰሩ ነው፡፡ ስለዚህ በእርግጠኝነት በጤና ጣብያዎችም ሆነ በሆስፒታሎች ደረጃ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ አሉ ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ማስተላለፍ የምፈልገው መልእክት የጤና ተቋማቱ በባለሙያም ይሁን በአቅርቦት ደረጃ የተሟሉ በመሆናቸው እናቶች በእርግዝና ጊዜ እየሔዱ ክትትል እንዲያደርጉና በጤና ተቋም በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲወልዱ ማድረግ ነው፡፡ የቅብብሎሽ ስርአቱም በጥሩ ሁኔታ የተዘረጋ ስለሆነ ምናልባት በጤና ጣብያ መውለድ የማይችሉ ከሆነ ወደሆስፒታል የሚተላለፉ በመሆኑ በዚህ ረገድ ምንም ስጋት ሊኖራቸው አይገባም ብዋል ዶ/ር ታዬ ቶሌራ፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 22ኛው አመታዊ ጉባኤ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ፌብረዋሪ 25/2014 ተጠናቆአል፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

በደሳለኝ ግርማ (ዲዶስ ሳምናስ) የተፃፉ የአጭር ልብወለድ እና የግጥም ስብስቦችን የያዘ መፅሃፍ በዛሬው ዕለት በሐረር ይመረቃል፡፡
በአንድ በኩል “አድናቂው” በሚል ርዕስ የአጭር ልብወለድ ስብስቦች ያካተተው መፅሃፉ፤ በሌላው በኩል “እግዜርና አፍሪካ” በተሰኘ ርዕስ የግጥም ስብስቦችን ይዟል፡፡ በኤች ዋይ ኢንተርናሽናል የህትመት ሥራ ድርጅት የታተመው መፅሃፉ፤ በ40 ብር ከ50 ለገበያ ቀርቧል፡፡

       አራት ሳምንታት ቢቆጠሩም የሳንዶር ኒድልማን ሞት ለማመን ከብዶኛል፡፡ የአስከሬን ማቃጠል ስነ-ስርዓቱ ላይ ስገኝ በወንድ ልጁ ጥያቄ መሰረት ሀባብ ይዤ ነበር፡፡ ሀሳቤ ግን እዚያ አልነበረም፡፡ በስፍራው የተገኘነው ብዙዎቻችን ለቀስተኞች የየራሳችንን ህመም ከማድመጥ በቀር ሌላ ሌላውን ሀሳብ ረስተን ነበር፡፡
ኒድልማን አስከሬኑ ስለሚቃጠልበት መንገድ እያቀደ በማሰላሰል ተጠምዶ ነበር፡፡ አንዴ እንዲያውም ያለኝን አልረሳውም፡፡ “ከመቀበር ብቃጠል ይሻለኛል፤ ቅዳሜና እሁድን ከሚስቴ ጋር ከማሳልፍም…”፡፡ በመጨረሻም እንዲያቃጥሉት ወሰነና አመዱን ለሄድልበርግ ዩኒቨርሲቲ ተናዘዘ፡፡ ኋላ ላይ ዩኒቨርሲቲው አመዱን በአራቱም አቅጣጫ ለነፋስ በትኖ፣ ጥቂት ያህል በስልቻው ውስጥ አስቀረ፡፡
የተጨማደደ ሱፉንና ግራጫ ሹራቡን እንደለበሰ ፊቴ ላይ ድቅን ይልብኛል፡፡ ብዚ ጊዜ በከባድ ሀሳቦቹ ስለሚዋጥ፣ ኮቱን ሲደርብ ከእነ ማንጠልጠያው ይለብሰው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የለበሰው ኮት ውስጥ ማንጠልጠያው መኖሩን ታዝቤ ብነግረው፣ ፈገግ ብሎ እንዲህ አለኝ፤ “ጥሩ ነዋ! ቲዮሪዎቼን የሚያጣጥሉ ሰዎች ቢያንስ ሰፊ ትከሻ አለው ብለው ያስቡ”፡፡
ኒድልማንን በቀላሉ መረዳት አዳጋች ነው፡፡ ጋግርቱ ከደንታቢስነት ተቆጠረበት እንጂ እሱስ ጥልቅ ሀዘኔታ የሚሰማው እሩህሩህ ሰው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ውስጥ የተከሰተ አስከፊ አደጋን ከተመለከተ በኋላ፣ አንድ ዋፍልስ ኬክ በልቶ ሁለተኛ መድገም አቅቶት ሁሉ ነበር፡፡ በዝምታው ምክንያት ሰዎች አይቀርቡትም፡፡ እሱ ግን “ንግግር የተበከለ የመግባቢያ መንገድ ነው” ብሎ ከፍቅረኛው ጋር እንኳ የሚግባባው በጽሑፍ ነበር፡፡
ከኮሎምቢያው ዩኒቨርሲቲ ዲን አይዘንአወር ጋር ተጋጭቶ ከስራው በተባረረ ጊዜ እኚህን የቀድሞ ጄነራል፤ የምንጣፍ መወልወያ ይዞ መንገድ ላይ ጠበቃቸውና አይዘንአወር መሸሸጊያ ፍለጋ አጠገባቸው ወደሚገኝ የአሻንጉሊት መሸጫ ሱቅ ሮጠው እስኪገቡ አባረሯቸው፡፡ (ከዚህ ቀደም እነኚህ ሁለት ሰዎች በደወል ትርጉም ቀላል ተከራክረዋል፡፡ የደወል ድምፅ የሚያመለክተው የአንድን ክፍለ ጊዜ መጠናቀቅ ይሁን የሌላ ክፍለ ጊዜን መጀመር በአደባባይ እንካ ሰላንቲያ ገጥመው ነበር፡፡)
ኒድልማን ሁሌም ቢሆን ሰላማዊ ሞትን ነበር የሚመኘው፡፡ “ልክ እንደ ወንድሜ ጆዋን፣ በመጻሕፍቶቼና በወረቀቶች መሀል…”ይላል… (የኒድልማን ወንድም የጠፋበትን መዝገበ-ቃላት ሲፈልግ ዴስክ ስር ታፍኖ ነበር የሞተው)፡፡
ግን ያ ሕንጻ ምሳ ሰዓት ላይ ሲፈራርስ፣ ኒድልማን ቆሞ እንደሚመለከትና የፍርስራሹ ፍንጣሪ አናቱን እንደሚቆጋው ማን አስቦ ነበር? ኩርኩሙ ታላቅ ድንጋጤ ፈጠረበትና ፊቱ ላይ ወፍራም ፈገግታ እያሳየ የህይወት ዘመኑን አገባደደ፡፡ ትንፋሹ ከመውጣቱ በፊት “አይ፤ አልፈልግም፡፤ ፔንጉይንማ በፊትም አለኝ” ብሏል፡፡
ኒድልማን በሞተበት ወቅት እንደተለመደው በርካታ ጉዳዮች ላይ እየሰራ ነበር፡፡ “መልካምና ሚዛናዊ ባህሪ የተሻለ ሞራላዊ ይዘት ያለው ብቻ ሳይሆን በስልክ ሊተገበርም ይችላል” በሚል ቲዮሪው ተመስርቶ አዲስ ዓይነት ስነ-ምግባር እየገነባ ነበር፡፡ ተጋምሶ የነበረው አዲስ የስነ-ትርጉም ምርምሩም፤ የአረፍተ ነገር መዋቅር በተፈጥሮ የሚታደል፣ ማማረር ግን በልምድ የሚገኝ መሆኑን ያረጋግጣል (ቢያንስ ሁልጊዜ ቱግ ቱግ እያለ ይሄንኑ ስለማረጋገጡ ይሞግታል)፡፡ በመጨረሻም፤ አንድ ሌላ መጽሐፍ ስለ ሆሎካስት አዘጋጅቷል፡፡ ስለ ክፋት ድርጊቶች አብዝቶ ሲጨነቅ የኖረው ኒድልማን፤ እውነተኛ ክፋት ሊደረግ የሚችለው የአድራጊው ሰው ስም “ብላኪ” ወይ ደግሞ “ፒቲ” የሚባል ከሆነ ብቻ እንደሆነ በርቱዕ አንደበቱ ይሞግት ነበር፡፡ ከብሔራዊ ሶሻሊዝም ሀሳብ ጋር የነበረው አጉል ቅብጠት በአካዳሚያዊ ክበባት ውጉዝ እንዲሆን አድርጎትም ነበር፡፡
በሂትለር ላይ ያለውን አቋም ለመንቀፍ በጣም ቀላል ነው፤ ግን ደግሞ ፍልስፍናዊ ጽሑፎቹን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ዘመናዊ ስነ-ህላዌን ሲነቅፍም ሰው (ምንም እንኳ የነበሩት አማራጮችቹ ውስን ቢሆኑም) ከዘላለማዊነት በፊት መኖሩን ሞግቷል፡፡ በኑሮ እና ኑሮ መካከል ልዩነቶችን ማየት ከመቻሉም በላይ አንደኛው መልካም እንደሆነ ለማወቅ ታድሎ ነበር፤ የትኛው እንደሆን ቆይቶ ለማስታወስ ቢቸግረውም፡፡ ለኒድልማን የሰው ልጅ ነፃነት ማለት የህይወትን ወለፈንድነት መረዳትን ያካትታል፡፡ “እግዜር ዝምተኛ ነው” ማለትን ያበዛ ነበር፡፡ “እንደው ግን ሰውንም ጭምር ፀጥ ማሰኘት ቢቻል ኖሮ!” ይላል።
ንጹህ ህላዌን መጎናፀፍ የሚቻለው በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ብቻ ነው፤ ያኔም ቢሆን መኪና መዋስ ያስፈልግሃል ብሎ ያስብ ነበር ኒድልማን፡፡ በእሱ አመለካከት የሰው ልጅ በተፈጥሮ ውስጥ የራሱ ሚና ኖሮት የሚንቀሳቀስ ፍጡር እንጂ፤ ከተፈጥሮ ተነጥሎ የሚታይ “ቁስ” አይደለም፡፡ እናም መጀመሪያ ምንም ያልተሰማው እንደሆነ በማስመሰል፤ ኋላ ላይ ግን ራሱን በጨረፍታ የማየት ተስፋ ሰንቆ ወደ ሌላኛው የክፍሉ ጥግ በፍጥነት ካልተንደረደረ በስተቀር የሰው ልጅ የራሱን ህልውና ሊታዘብ አይቻለውም፡፡
ለህይወት ሂደት የሰጠው አንድ ስያሜ “አንግስት ዜይስት” ይሰኛል፤ በግርድፉ ሲተረጎም የጭንቅ ወቅት እንደማለት፡፡ በእርግጥ ድርጊቱ የሚከናወነው ጊዜ በሚለው ፅንሰ ሀሳብ ውስጥ ባይሆንም ሰው ማለት ጊዜ ውስጥ እንዲኖር የተፈረደበት ፍጡር መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ከብዙ አሰላስሎት በኋላ ኒድልማን በምሁራዊ ምጥቀቱ ተመርቶ አለመኖሩን ተረዳ፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ባልንጀሮቹም እንደሌሉና እውን የሆነው ብቸኛው ነገር ስድስት ሚሊዮን ብር የተበደረበት የባንክ ሰነድ ብቻ መሆኑ ተገለፀለት፡፡ ቆይቶ ብሄራዊ ሶሻሊዝምን እንደማይደግፍ በግልጽ መታወቅ ሲጀምር ከበርሊን ኮበለለ፡፡ በቅጠላ ቅጠል እየተሸሸገና ሶስት ፈጣን እርምጃዎችን ወደ ጎን ወደ ጎን ብቻ እየተራመደ ማንም ሳያውቀው ድንበሩን ተሻገረ፡፡
አውሮፓ ውስጥ በሄደበት ሁሉ ተማሪዎችና ምሁራኑ ሁሉ መልካም ስምና ዝናውን በማሰብ በማናቸውም ነገር ሊተባበሩት ይጓጉ ነበር፡፡ በስደት ሆኖ “ጊዜ፣ ትርጉም እና ዕውነታ፣ የምንነት ስልታዊ መገለጥ” የሚለውን መጽሐፉንና ከዚህ ቀለል የምትለውን “በሚሰወሩ ወቅት ሊመገቡባቸው የሚችሉ ምርጥ ምግብ ቤቶች” የምትል አዝናኝ መጽሐፉን ለማሳተም ጊዜ አግኝቷል፡፡ ቼይም ዊዝማን እና ማርቲን ባቤር ኒድልማን ወደ አሜሪካ እንዲሄድ የሚያስፈቅድለት ፒቲሽን ቢያስፈርሙለትም እንኳ በወቅቱ አሜሪካ እንደደረሰ ሊያርፍበት የፈለገው ሆቴል፣ ያልተያዘ ክፍል የሌለው ስለነበር ጉዳዩ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ፕራግ ውስጥ ከተደበቀበት ቦታ የጀርመን ወታደሮች ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው፣ ወደ አሜሪካ ለመምጣት ወሰነ፡፡ ሆኖም ትኩረት የሚስብ አንድ ትዕይንት በአውሮፕላን ማረፊያው ተከሰተ፣ አውሮፕላኑ ከተፈቀደለት ጭነት በላይ ነበር የያዘው። በዚያው በረራ ላይ የነበረው አልበርት አንስታይን፣ ኒድልማን ጫማዎቹ ውስጥ የወሸቃቸውን የጫማ ቅርፅ ማስጠበቂያ እንጨቶች ቢያወጣቸው ኮተቱን በሙሉ መጫን እንደሚችል አብራራለት፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለቱ በርካታ ደብዳቤዎችን ተጻጽፈዋል፡፡ በአንድ ወቅት አንስታይን እንዲህ ሲል ጽፎለታል፤ “ያንተ ሥራ እና የኔ ሥራ በጣም ይመሳሰላሉ፤ ምንም እንኳ ያንተ ሥራ ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ባልችልም”
በአሜሪካ ቆይታው በአንድ ወቅት ከህዝብ አፍ ሲጠፋ “አለመኖር በድንገት ቢያጋጥምዎት ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጠቃሚ ክሮች” የምትል መፅሐፍ አሳተመ፡፡ በተጨማሪም Semantic Modes of Non-Essential Functioning የሚል ሌላ መጽሐፍ አሳትሞ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ፊልም ተሰርቶበታል።
ከኮሚኒስት ፓርቲ ጋር በነበረው ግንኙነት ምክንያት ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ እንዲለቅ ተጠይቆ ነበር፡፡ ዕውነተኛ ነጻነት መገኛዋ ኢኮኖሚያዊ እኩልነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ ብቻ መሆኑን ገልፆ፣ የጉንዳኖችን አኗኗር እንደ አርአያነት ጠቅሷል፡፡ ጉንዳኖችን ለሰዓታት ያህል በቁጭታዊ ተመስጦ ካስተዋለ በኋላ “የምር ተቀናጁ እኮ ናቸው! ብቻ ሴቶቻቸው ትንሽ ከዚህ የተሻለ ውበት ቢኖራቸው እንዴት ስኬታማ በሆኑ!” ይል ነበር፡ በሚገርም ሁኔታ የሀገሪቱ ምክር ቤት ኒድልማን ፀረ-አሜሪካ ተሟጋች መሆኑን ሲበይንበት፣ የራሱን ፍልስፍና እየጠቀሰ ወደ ሥራ ባልደረቦቹ አላከከባቸው፡፡ “ፖለቲካዊ ድርጊቶች ከዕውነተኛ ህላዌ ውጭ ሊኖሩ ከመቻላቸውም በላይ የሚያስከትሉት ምንም ዓይነት የሞራል ጣጣ የለውም” ብሏል፡፡ በዚህ ጊዜ አካዳሚያዊ ማህበረሰቡ ለተወሰኑ ሳምንታት ቅጣት ውስጥ ቢቆይም ወዲያው ፕሪኒስተን የሚገኘው ፋካልቲ ዋጋውን ሊሰጠው ወሰነ፡፡ ኒድልማን በሰበቡ የነጻ ፍቅር እሳቤውን ለማስረዳት ይሄንኑ አመክንዮ ተጠቀመ፤ ሆኖም ከሞከራቸው ሁለት ተማሪዎች አንዷም አምነው አልተቀበሉትም፤ እንዲያውም የአስራ ስድስት አመቷ ታዳጊ አጋለጠችው፡፡
የኒዩክሌር ሙከራዎች እንዲቋረጡ ተግቶ ይሰራ ነበረው ኒድልማን፤ ወደ ሎስ አላሞስ በመብረር በዚያ ከሚገኙ በርካታ ተማሪዎች ጋር በማበር ከአንድ ቀድሞ ከታቀደ የኒዩክለር መሞከሪያ ሥፍራ ላለመንቀሳቀስ አድማ መቱ፡፡ ደቂቃዎች ተቆጥረው ሙከራው እንደማይቋረጥ ግልፅ ሲሆን ኒድልማን “ኦ ኦ” ሲል ተሰማና ወዲያውኑ እግሬ አውጭኝ አለ። ጋዜጦቹ ያልዘገቡት ነገር ቀኑን ሙሉ እህል የሚባል አለመቅመሱን ነበር፡፡      
በሕዝብ የሚታወቀውን ኒድልማን ማስታወስ ቀላል ነው፡፡ ብሩህ፣ ቁርጠኛ ደራሲ፡፡ እኔ ግን ግለሰቡን ኒድልማን ነው ሁሌም በደስታ የማስታውሰው። ሁሌም ምርጥ ኮፍያ የሚያደርገውን ሳንዶር ኒድልማን። አስከሬኑ ሲቃጠልም ኮፍያ አድርጎ ነበር፡፡ እንዲህ በማድረግ የመጀመሪያው ሰው ይመስለኛል፡፡ የማስታውሰው የካርቱን ፊልም አብዝቶ የሚወደውን፤ ስለ አኒሜሽን በቂ ማብራሪያ በማክስ ፕላንክ ቢሰጠውም ሚኒ ማውስን ለፍልሚያ የጋበዘውን ኒድልማን ነው፡፡
ኒድልማን በእንግድነት ቤቴ በቆየበት ወቅት፣ አንድ የሚወደው ዓይነት ቱና (የታሸገ ዓሳ) እንዳለ በመረዳቴ፣ የእንግዳ ክፍሉን ማብሰያ ቤት በዚሁ ዓይነት ቱና ሞላሁት፡፡ የቱና ፍቅሩን ለእኔ ለመግለፅ ቢያሳፍረውም አንዴ ብቻውን ሆኖ ሁሉንም ጣሳዎች ከፍቶ “ሁላችሁም ልጆቼ ናችሁ” ሲል ሰማሁት፡፡
የኒድልማንን ሰባኛ ዓመት የልደት በዓል አስታውሳለሁ፡፡ ሚስቱ ፒጃማ ነበር የገዛችለት፡፡ አዲስ መርሴዲስ እንድትገዛለት ፍንጭ ሲሰጣት ስለከረመ በግልፅ በሚታይ መልኩ ተበሳጭቶ ነበር፡፡ ብቻውን ወደ ማንበቢያ ክፍሉ ሄዶ፣ እንደ ሕፃን ልጅ መነፋረቅና መደንፋቱ እስከዛሬም ድረስ መለያው ሆኖ የሚታወስ ነው፡፡ ቆይቶ ግን በፈገግታ ተሞልቶ ወደ ግብዣው ተመለሰ፡፡ ፒጃማውንም ሁለት አጫጭር ተውኔቶች በሚመረቁበት ምሽት ለብሶ ታየ፡፡

Published in ልብ-ወለድ

የ“ፔን ኢትዮጵያ” የሦስት ዓመት ጉዞ በጨረፍታ  

“ፔን ኢንተርናሽናል” አርማው ሉል ነው። ዓለምን በሚወክለው ሉል ላይ የተለያዩ አገራት ለጽሑፍ ከሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች የተወሰዱ ፊደላት ታትመዋል፡፡ ከአማርኛ ቋንቋም ቃ፣ ሁ፣ ል፣ ሂ … ሆሄያት በሉሉ ላይ ከሚታዩ ፊደላት ጋር ተካትተዋል፡፡ ይሄ ዓይነት ዕድል የተገኘው “ፔን ኢትዮጵያ” በአገራችን በመቋቋሙ የተነሳ ሲሆን ማህበሩ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ተመዝግቦ በየካቲት ወር 2002 ዓ.ም ነው ዕውቅና ያገኘው፡፡
ዓለምአቀፉ “ፔን ኢንተርናሽናል” ከተመሰረተ ከ90 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ከአንድ መቶ በላይ በሚሆኑ የተለያዩ አገራት 150 የሚደርሱ አቻ ማህበራትም ተመስርተዋል፡፡ የ “ፔን ኢንተርናሽናል” ምሥረታ ታሪክ የሚጀምረው ከእንግሊዝ ነው። ዋናው ድርጅት አሁን ላለበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ታሪኮችን አሳልፏል። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ ዓለምን በሁለት ጎራ በከፈለው የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን … በርካታ ውጣ ውረዶችን የመጋፈጡን ያህል ቀላል የማይባሉ ስኬቶችንም ተቀዳጅቷል፡፡
ማህበሩ መጀመሪያ ሲመሠረት “Pen” የሚል መጠሪያ ነበረው፡፡ ምህፃረ ቃሉ የሚወክለውም ገጣሚያን፣ ወግ ፀሃፊያንና ደራሲያንን  ነበር፡፡ ማህበሩ ከተመሠረተ በኋላ አቻ ክበባትን በተለያዩ አገራት በአጭር ጊዜ እያስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት የ“Pen” ስያሜና ትርጓሜ ላይ ለውጥ ተደረገ። ምህፃረ ቃሉ የሚወክለው ትርጓሜም ከሦስት ወደ አምስት አደገ፡፡ የቃሉ ውክልና ለገጣሚያን፣ ለፀሃፌ ተውኔቶች፣ ለአርታኢዎች፣ ለወግ ፀሃፊዎችና ለደራሲያን እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ መጠሪያውም “ፔን ኢንተርናሽናል” ተባለ፡፡
ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ አቋም ያለው ፔን ኢንተርናሽናል፤በሁሉም አገራት የሚቋቋሙት አቻ ማህበራቱ በጋራ የሚያከናውኑት ግልጽ አላማዎች ቀርፆ ይንቀሳቀሳል፡፡ ማንበብና መፃፍን ያበረታታል፡፡ ሐሳብ የመግለጽ ነፃነት እንዲስፋፋ ይተጋል፡፡ ቋንቋና ባህል እንዲጎለብት ይጥራል፡፡ የዓለም ሠላም አስተማማኝ እንዲሆንና እንዲዳብር ይሰራል፡፡ ምሁራዊ የክርክር መድረኮች እንዲስፋፉ ያበረታታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የትምህርት ዕድል ያላገኙ ወጣቶችና ጎልማሶች መማር እንዲችሉ፤ የመፃሕፍት እጥረት ላለባቸው የተተረጎሙ ጥራዞችና ቤተ መፃሕፍት እንዲያገኙ፤ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የፔን ኢንተርናሽናል አቻ ማህበር አባላት አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ስልጠና መስጠትና የሀሳብ ልውውጥ ማድረጊያ መድረኮችንም ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ፡፡
ይህንን ዓላማ መሠረት በማድረግም የፔን ኢንተርናሽናል አቻ ክበባት ባሉባቸው አገራት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ስለ ሰብአዊ መብት ለማስተማር በማእከላዊ እስያ፣ ታዳጊዎችን ማትጊያ መድረክ በጋና፣ ወጣት ፀሐፊያንን ለማበረታታት በሀይቲ፣ ማንበብና መፃፍን ለማነቃቃት በማላዊ፣ ስነ ጽሑፍን ለማስተማር በኔፓል፣ ለሕፃናት መፃሕፍትን ተርጉሞ ለማቅረብ በደቡብ አፍሪካ፣ ተንቀሳቃሽ ቤተ መፃሕፍት ለማደራጀት … በፊሊፒንስና መሰል አገራት የተከናወኑ ተግባራት ይጠቀሳሉ፡፡
በፔን ኢንተርናሽናል ስር ከተቋቋሙት ዓለም አቀፍ ክበባት አንዱ የሆነው “ፔን ኢትዮጵያ” በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ዕውቅና ከተሰጠው በኋላ ሥነ ጽሑፍን ርዕስ ያደረጉ ሦስት መድረኮችን አዘጋጅቷል፡፡ በ2004 ዓ.ም “ንባብን ማስፋፋት”፣ በ2005 ዓ.ም “ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ትርጉም ያበረከተው አስተዋጽኦ”፣ በ2006 ዓ.ም ደግሞ “ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት እና ሥነ ጽሑፍ በኢትዮጵያ” በሚሉ ዋነኛ ርዕሶች ስር ተዛማጅ ጉዳዮችን በማካተት ነበር ፕሮግራሞቹ የተከናወኑት።
ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም የተካሄደውን ጨምሮ ሦስቱም መድረኮች አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ባህል ማዕከል አዳራሽ ነው የተስተናገዱት፡፡ “ፔን ኢትዮጵያ” በሦስት ተከታታይ ዓመታት ካሰናዳቸው ክንውኖች የ2004 እና የ2005 ዓ.ም ፕሮግራሞች በምን መልኩ ተግባራዊ እንደሆኑ የሚያመለክቱ ሁለት ዳጎስ ያሉ መፃህፍትን  አሳትሞ አሰራጭቷል፡፡
የ“ፔን ኢትዮጵያ” ፕሬዚዳንት የአቶ ሰለሞን ኃ/ማርያምን ጨምሮ ከፔን ኢንተርናሽናልና ከተለያዩ አገራት አቻ ማህበራት ተወክለው የመጡ እንግዶች የተለያዩ ንግግርና መልዕክት ማስተላለፋቸውን የሚያመለክቱት የጉባኤ ዘገባዎቹ፤ በእያንዳንዱ መድረክ የተጋበዙ ምሁራን ያቀረቧቸው የጥናት ወረቀቶች፣ ጥናቶቹ ከቀረቡ በኋላ ከተሳታፊዎች የተሰነዘሩ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን፣ እንዲሁም በመድረኩ የቀረቡ ግጥሞች በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ቀርበውባቸዋል፡፡
በየካቲት ወር 2004 ዓ.ም በተሰናዳው የመጀመሪያ መድረክ ከአዲስ አበበ ዩኒቨርስቲ የተጋበዙት አብርሃም ዓለሙ “የንባብ ባህል በኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚዎቹና ተግዳሮቶች”፤ ተፈሪ ንጉሴ ደግሞ “የሥነ-ጽሑፍ ህትመት ውጤቶች ዋና ዋና ምቹ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ ያዘጋጁትን የጥናት ፅሁፎች አቅርበዋል። በ2005 ዓ.ም በተሰናዳው ሁለተኛ መድረክም “የትርጉም ሚና በኢትዮጵያ” በደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም እና “ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ትርጉም ያበረከተው አስተዋጽኦ” በሚል ደግሞ በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ሁለት የጥናት ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በቀረበው የ“ፔን ኢትዮጵያ” ሶስተኛ መድረክም ተመሳሳይ መርሃ ግብር ተካሂዶበታል፡፡
“ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት እና ሥነ ጽሑፍ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን የ“ፔን ኢንተርናሽናል”ን አቻ ክበባት ወክለው ከተለያዩ አገራት ከመጡት እንግዶች ሁለት እንስት ፀሐፍት “ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ከዓለም አቀፍ ዕይታ አንፃር” በሚል ርዕስ ያሰናዱትን በውይይት መልክ አቅርበዋል፡፡
የ“ፔን ኢትዮጵያ” ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ኃይለማርያም እንዳመለከቱት፤ ማህበሩ የ5 ዓመት እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡  የተለያዩ ችግሮች ቢገጥሙትም የተለያዩ አካላት ባደረጉት ትብብርና እገዛ ሶስቱ ተከታታይ ዝግጅቶች እውን መሆን ችለዋል፡፡ በየመድረኮቹ ከቀረቡት ንግግሮች መረዳት እንደሚቻለው፤ የኢትዮጵያን ሥነ-ጽሑፍና ፀሀፍትን ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር ለማስተዋወቅ “ፔን ኢትዮጵያ” ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተስፋ ተጥሎበታል።
ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም “የትርጉም ሚና በኢትዮጵያ” በሚለው ጥናታዊ ፅሁፋቸው፤ የኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ ስራዎችና ፀሀፍት በአገር ውስጥ ብቻ ተወስነው መቆየታቸውን አመልክተዋል፡፡
“ከአገራዊ ቋንቋ ወደ ውጭ አገር ቋንቋ የተተረጎሙ ስራዎች” በሚል ንዑስ ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍም፤ በዘርፉ የሚያኮራ ስራ አለመሰራቱን ደራሲው ጠቁመዋል፡፡ የጥናት ጽሑፍ አቅራቢውን ጨምሮ የመንግስቱ ለማ፣ የከበደ ሚካኤል፣ የሀዲስ አለማየሁ፣ የአማረ ማሞ፣ የበዓሉ ግርማ፣ የብርሃኑ ዘሪሁን፣ የአስፋው ዳምጤ፣ የዳኛቸው ወርቁና የመሳሰሉ ጥቂት ፀሃፍት ስራዎች ወደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ሩሲያና ኖርዊጂያን ቋንቋዎች መተርጎማቸውም ተገልጿል፡፡ ይህንን ትልቅ ክፍተት ለመድፈን “ፔን ኢትዮጵያ” ላይ ተስፋ ተጥሏል፡፡ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ኃ/ማርያም ባቀረቡት ንግግር “በኢትዮጵያዊያን አንጋፋና ብርቅዬ የረዥም ልብ ወለድ ፀሀፊዎች፣ ፀሐፊ ተውኔቶች፣ ተርጓሚያንና ገጣሚያን… የተሰሩ በርካታ ስራዎች መኖራቸው ሐቅ ቢሆንም ዓለም ግን እነዚህን ጠቃሚ ኢትዮጵያዊ የስነ ጽሑፍ ስራዎች ሊጋራን ወይም ሊቋደሰን አልቻለም” ብለዋል፡፡
ከአቻ ማህበራት ተወክለው በመድረኩ ላይ ከተሳተፉት የውጭ ዜጎች መካከል የዓለም አቀፉ ፔን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጆን ራልስተን ሶል “ኢትዮጵያዊያን ፀሐፍት በምንም አይነት ሁኔታ ላይ ቢገኙ ፔን ዓለም አቀፍን በመቀላቀላቸው የዓለም አቀፍ ፀሐፍት ቤተሰብ አባላት መሆናቸው እርግጥ ነው” በማለት ክፍተት መድፈኛው መንገድ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡
የታቀዱትና የታለሙት ምን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ የሚለውን ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል። “ፔን ኢትዮጵያ” ባዘጋጃቸው ሶስት መድረኮች ግን የኢትዮጵያ ሥነፅሁፍ የዓለም የሥነፅሁፍ መድረክን መቀላቀል እንደሚችል የተስፋ ጭላንጭል  ታይቷል።
ኢትዮጵያዊያን የስነ-ጽሑፍ ቤተሰቦች ከኖርዌይ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጃፓን… ከመጡ አቻዎቻቸው ጋር በጋራ ቁጭ ብለው መክረዋል፡፡ ዓለም አቀፉን የፀሐፍት መድረክ መቀላቀል እንደሚቻል ይህ አንዱ ምልክት ይመስላል፡፡

Published in ጥበብ
Page 11 of 17