“ምርጫውን ያራዘሙት ሽንፈት ስላሰጋቸው ነው” ተቃዋሚዎች
*የአሜሪካና እንግሊዝ መንግስታት ምርጫው መራዘሙን ተቃውመዋል


በዛሬው ዕለት ይከናወናል ተብሎ ቀን የተቆረጠለትን የናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ለስድስት ሳምንታት አራዝመዋል በሚል በአለማቀፍ ደረጃ ትችት እየተሰነዘረባቸው ያሉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፣ ምርጫውን አላራዘምኩም ሲሉ አስተባበሉ፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፤ ፕሬዚዳንቱ ምርጫውን ለማራዘም በተላለፈው ውሳኔ ውስጥ እጃቸው እንደሌለበትና ውሳኔውን ያስተላለፉት አካላት በጉዳዩ ዙሪያ እንዳላማከሯቸው አስታውቀዋል፡፡
የአገሪቱ የምርጫ አስፈጻሚ ባለስልጣናት፣ ቦኮ ሃራም የተባለው ጽንፈኛ ቡድን ምርጫውን የሚያስተጓጉል ድርጊት ሊፈጽም ይችላል በሚል ከጸጥታ ሃይሎች የተገለጸላቸውን ስጋት መነሻ በማድረግ ምርጫው ለስድስት ሳምንታት እንዲራዘም መወሰናቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
የናይጀሪያ ምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ አታሂሩ ጃጋ፣ ምርጫው ሊራዘም የቻለው መራጮችን ከቦኮ ሃራም ከሚሰነዘሩ የሽብር ጥቃቶ መከላከል የሚችል በቂ የጸጥታ ሃይል ባለመኖሩ ነው ቢሉም፣ በምርጫው ለመወዳደር የተዘጋጁ የአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ምርጫውን ያራዘሙት እንዳይሸነፉና ስልጣናቸውን እንዳይነጠቁ በመስጋት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን እና ፓርቲያቸው ፒዩፕልስ ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ ከቀድሞው የአገሪቱ የጦር መሪ ሙሃማዱ ቡሃሪ እና ኦል ፕሮግሬሲቭስ ኮንግረስ ከተሰኘው ተፎካካሪ ፓርቲ ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ዘገባው፤ቡሃሪ በስልጣን ላይ ያለው የጆናታን መንግስት የቦኮ ሃራምን የጥፋት እንቅስቃሴ ለመግታት አቅምም ሆነ ፈቃደኝነት ይጎድለዋል ሲሉ መተቸታቸውንና እሳቸው ስልጣን ላይ ከወጡ ቦኮ ሃራምን በወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠፉ ቃል መግባታቸውን ጠቁሟል፡፡
የናይጀሪያ መንግስት ምርጫው መራዘሙን ማስታወቁን ተከትሎ፣ ውሳኔው በአለማቀፍ ደረጃ እየተተቸ እንደሚገኝ የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት በበኩሉ፤የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በአገሪቱ ያሉ የጸጥታ ስጋቶች ምርጫን ለማራዘም በቂ ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም ማለታቸውን ጠቁሟል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ጸሃፊ ፊሊፕ ሃሞንድ በበኩላቸው፤ ናይጀሪያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት የምንደግፍ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ያለው የጸጥታ ችግር ናይጀሪያውያን ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዳይጠቀሙ ለማገድ ምክንያት ሊሆን አይገባም በማለት ምርጫው መራዘሙን ተችተዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ   በማርኬቲንግ እንቅስቃሴው ተስተካካይ በማጣት ቀጥሏል፡፡ የፕሪሚዬር ሊጉ አስተዳደር በቴሌቭዥን  ገቢው የሪኮርድ  ገቢ ያገኘበትን የስምምነት ውል  ከሰሞኑ የፈፀመ ሲሆን፤  የስርጭት መብቱን  ስካይ ቲቪና ቢቲ የተባሉ የብሮድካስት ኩባንያዎች በ7.8 ቢሊዮን ዶላር ገዝተውታል፡፡ ሁለቱ ብሮድካስት ኩባንያዎች እስከ 2019 እኤአ ሊጉን በቀጥታ የቴሌቭዥ ስርጭት ሽፋን ለመስጠት ተስማምተዋል፡፡ ስካይ ቲቪ  168 ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ  በ5.9 ቢሊዮን ዶላር ክፍያ የተዋዋለ ሲሆን የተቀሩትን 42 ጨዋታዎችን ለማሰተላለፍ ያሸነፈው ቢቲ እስከ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ይከፍላል፡፡ በአጫጭር የዘገባ ሽፋኖች የመስራት ውል የፈፀመው ቢቢሲ 311 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል የሚፈልገውን ድርሻ አግኝቷል፡፡   በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ የሆኑገ 20  ክለቦች ከቴሌቭዥን የስርጭት  መብት ከሚገኝ ገቢ 50 በመቶውን  ድርሻ እንደውጤት ደረጃቸው  ተሰልቶ መካፈላቸው ከፍተኛ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡ ሌላው 25 በመቶው ለሊጉ የገንዘብ ሽልማት የሚቀርብ ሲሆን የተቀረው 25 በመቶው ስኬታማ የቴሌቭዥ ስርጭቶችን ለማከናወን በበጀት መልክ እንደሚወጣ  ታውቋል፡፡ በቴሌቭዥን የስርጭት መብት  ገቢው የእንግሊዝ ክለቦች በየዓመቱ  ገቢያቸው በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ላይ ናቸው፡፡ ከሌሎች የአውሮፓ ክለቦች ጋር ለማነፃፀር በሚያስቸግር ትርፋማነት ውስጥ እየተወዳደሩ ናቸው፡፡ ታዋቂው የቢዝነስ ጥናት እና ምርምር ተቋም ዴሊዮቴ በሚሰራው የገበያ ጥናት በተሰራው የዓለም ፕሮፌሽናል ክለቦች የገቢ ደረጃ ውስጥ እስከ 40ኛ ባለው ቦታ 20 የእንግሊዝ ክለቦች መገኘታቸው ማስረጃ ይሆናል፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በሚቀጥሉት 3 ዓመታት በየውድድር ዘመኑ 2.6 ቢሊዮን ዶላር ከቴሌቭዥን ስርጭት መብት  እያገኘ የሚቀጥል ሲሆን ከዓለም በገቢው ከፍተኛ የሆነው የአሜሪካው ፉትቦል ሊግ ኤነኤፍኤል ለሚቀጥሉት 7 የውድድር ዘመናት  በየዓመቱ የሚያስገባው 7 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሊነፃፀርበት የሚችል ነው ፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በቲቪ ገቢ ብቻ ሳይሆን በስታድዮም ትኬት ሽያጭ፤ በማራኪ ሜዳና የስርጭት ፐሮግራም አካሄድ የማርኬቲንግ እድሎቹ  ከሌሎች የአውሮፓ አገራት አንፃር ተስተካካይ  እያጣ ነው፡፡ አሁን ሰሞኑን በተፈረመው አዲስ የቴሌቭዥ የስርጭት መብት ውል መሰረት 70 በመቶ ያደገው የፕሪሚዬር ሊጉ ገቢ የሻምፒዮን ክለብ ድርሻን ወደ 200 ሚለዮን ዶላር ሊያደርስ ከመቻሉም በላይ የመጨረሻው ወራጅ ድርሻ እስከ 110 ሚለዮን ዶላር  መጠጋቱ እንደማይቀር አመልክቷል፡፡ ይህ አይነቱ የገቢ እድገት የክለቦችን አቅም ሲያጠናክርም በፕሪሚዬር ሊጉ ሪከርድ የተጨዋቾች ደሞዝ 500 ሺ ዶላር መግባቱ አይቀርም ተብሏል፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በዓለም እግር ኳስ ገበያ እያገኘ ያለው ትርፋማነት የሚቀጥል ከሆነ እስከ 2019 እኤአ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የቲቪ ገቢ 13 ቢሊዮን ዶላር ሊገኝበት እንደሚችል ተነግራል፡፡ ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሃያ ክለቦች 11 በትልልቅ ኢንቨስተሮች መያዛቸውና ትርፋማ መሆናቸው የገበያውን ሁኔታ  እንደሟሟቀ እየተገለፀ ሲሆን ተጨማሪ ኢንቨስተሮችን በመሳብ ፕሪሚዬር ሊጉ ይጠናከራል፡፡
ባለፈው የውድድር ዘመን በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚወዳደሩ 20 ክለቦች የቴሌቭዥን ስርጭት መብት ጠቅላላ ገቢ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ተካፍለዋል፡፡ ከፍተኛውን ገቢ ያገኙ 6 ክለቦች ሊቨርፑል 150.2 ፤ ማንችስትር ሲቲ 148.8፤ ቼልሲ 145.7 አርሰናል  143.1፤ ቶትንሃም 138.1 እንዲሁም ማንዩናይትድ 137.1 ሚሊዮን ዶላር ድርሻ ነበራቸው፡፡ ከፕሪሚዬር ሊጉ የወረዱት ሶስት ክለቦች ደግሞ በአማካይ 97.02 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ነበራቸው፡፡
በሴሪኤ በቲቪ ስርጭት መብት 1.03 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ እየተገኘ ለ3 ውድድር ዘመናት ይቀጥላል፡፡ የውሉ ባለቤቶች የሩፐርተ መርዶክ የሆነው ስካይ እና የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር በርልስኮኒ ንብረት የሆነው   ሚዲያሴት ገዝተውታል ፣ እጥፉ ድርሻ የስካይ ቲቪ ነው ፡፡ የጣሊያን ሴሪኤ ባለፈው የውድድር ዘመን ከብሮድካስት ያስገባው 965.43 ሚሊዮን ዶላር  ሲሆን ሻምፒዮን የነበረው ጁቬንትስ 107.3  ሚሊዮን ዶላር ሲያገኝ ሌሎቹ ክለቦች ከፍተኛውን 92.4 ዝቅተኛውን 20.24 ሚሊዮን ዶላር ወስደዋል፡፡
በስፔን ክለቦች ድርድር የሚደርጉት በተናጠል ነው፡፡ ሩቡ ገቢ ከስፔን ውጭ ነው፡፡ ላሊጋው በየዓመቱ  905 ሚሊዮን ዶላር በቲቪ ስርጭት መብት ያስገባል፡፡ ከሁለት የውድድር ዘመናት በሃላ  ወደ ቢሊዮን ይደርሳል፡፡ የስፔኑ ላሊጋ 20 ክለቦች የተካፈሉት ደግሞ 862.4 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ሁለቱ ሃያል ክለቦች ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና 50 በመቶውን ድርሻ በመውሰድ ከሌሎች ተወዳዳሪ ክለቦች ከ3 እስከ 5 እጥፍ ብልጫ ያለውን የ160 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በነፍስው ወከፍ ተቀራምተዋል፡፡ ሌሎቹ የስፔን ክለቦች የነበራቸው ገቢ ከፍተኛው 54.8 ዝቅተኛው 20.54 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡
የፈረንሳይ ሊግ 1 በቲቪ ስርጭት መብት ብዙ አልተሳካለትም፡፡ ካናል ፕላስ እና ብሌን ስፖርትስ ለሚቀጥለው 2 ዓመት ውድድሩን የማስተላለፍ መብትን  የገዙት  በየዓመቱ  በ686 ሚሊዮን ዶላር  ለመክፈል ተስማምተው ነው፡፡ፒኤስ ጂ ሻምፒዮን ሆኖ ያገኘው ከፕሪሚዬርግ በመጨረሻነት የወረደ ክለብ  ከነበረው ገቢ በእጥፍ ያነሰ ነው
የፈረንሳዩ ሊግ 1 ደግሞ ገቢው 554.3 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን ሻምፒዮን የነበረው ፒኤስጂ 50.89 ሚሊዮን ዶላር ሲያስገባ ሌሎቹ ክለቦች ከፍተኛውን 47.63 እንዲሁም ዝቅተኛውን 14.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል፡፡
ቦንደስ ሊጋው በጀርመኑ ስካይ ቲቪ ስርጭት መብት  ኮንትራቱ  ለ2 ዘመናት ይቆያል፡፡ 550 ሚሊዮን  ዶላር በየዓመቱ በቲቪ ስርጭት መብት  ማስገባቱን በእጥፍ ለማሳደግ ታስባል፡፡በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ከቴሌቭዥ የስርጭት መብት የገባው 564 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ባየር ሙኒክ 42.1 እንዲሁም ዶርትመንድ 40.51 ሚሊዮን ዶላር ድርሻ ሲያገኙ ሌሎች ክለቦች ከ38.5 እስከ እስከ 20.02 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏቸዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት በ2015 የዴሊዮቴ የክለቦች ሃብት  ሊግ ለ18ኛ ጊዜ የወጣ ሲሆን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሃያ ክለቦች 50 በመቶውን ተቆጣጠረዋል፡፡ የዓለም 20 ሃብታም ክለቦች ዓመታዊ ገቢ በ1 ቢሊዮን ዶላር ጨምሮ 8 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን በዚህ እድገት የእንግሊዝ ክለቦች የአንበሳውን ድርሻ አግኝተዋል፡፡
የ2015 የሃብት ሊግ በሚሊዮን ዶላር
ሪያል ማድሪድ 707.63
ማንችስተር ዩናይትድ 667.13
ባየር ሙኒክ 627.9
ባርሴሎና 624.01
ፓሪስ ሴንት ዠርመን 610.61
ማንችስተር ሲቲ 533.61
ቼልሲ 499.6
አርሰናል 462.77
ሊቨርፑል 393.93
ጁቬንትስ 359.74

ለ31ኛው ግን የአዘጋጅም ፍንጭ  የለም
30ኛው አፍሪካ ዋንጫ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን የተለያዩ ዘገባዎች እየገለፁ ሲሆን፤ ለሚቀጥለው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ አገር እስካሁን አለመታወቁ አሳሳቢ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ፕሬዝዳንት የሆኑት ደቡብ አፍሪካዊቷ ዶክተር ናኮሶዛ ሲያማኒ ዙማ የኢቦላ ስጋትን ድል በማድረግ በተሳካ ሁኔታ የአፍሪካ ዋንጫ መዘጋጀቱን ጠቅሰው ኢኳቶርያል ጊኒ እና የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኦብያንግ ኑጉዌማ እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ውድድሩ የአህጉሪቱን አንድነት እና ሉዓላዊነት በማንፀባረቅ ለተጫወተው ሚና በአድናቆት አመስግነዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፈረንሳዊው ሄርቬ ሬናርድ  የአፍሪካ ዋንጫ ከሁለት የተለያዩ ቡድኖች ጋር በአስጨናቂ የመለያ ምቶች ማሸነፋቸውን የማይረሱት ታሪክ እንደሚሆንባቸው ተናግሯል፡፡ከብሄራዊ ቡድን ጋር የዋንጫ ድል ማስመዝገብ ለማመን የሚያስቸግር ደስታ እንደሚሰጥ የተናገረው ደግሞ የኮትዲቯር አምበል የነበረው ያያ ቱሬ ነው፡፡ ለስምንት ዓመታት በቆየበት የብሄራዊ ቡድን ልምድ ህልሙ ይህን የመሰለ ታላቅ ስኬት ማግኘት እንደነበር  ቱሬ አስታውሷል፡፡ ካፍ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በአፍሪካ ዋንጫው ኮከቦች ምርጫ ጋና በአራት ሽልማቶች ከፍተኛውን ድርሻ ስትወሰድ የዋንጫው አሸናፊ ኮትዲቯር ደግሞ በውድድሩ ምርጥ ቡድን  7 ተጨዋቾች በማስመረጥ ብልጫ አሳይታለች፡፡
 በተያያዘ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መገበደጃ ሰሞን በ2017 እኤአ እና በ2018 እኤአ ለሚደረጉት የአፍሪካ እና የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ያለውን ማጣርያ ሂደት ይፋ አድርጓል፡፡ ካፍ እንዳስታወቀው ከ3 ሳምንታት በሃላ በ2017 እኤአ ላይ 31ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ የሚያዘጋጅ አገር እንደሚታወቅ ሲሆን ወደዚህ ውድድር ለማለፍ የሚደረገው የምድብ ማጣርያ ድልድልም ይገለፃል፡፡ሞሮኮ በ2017ና በ2019 ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች እንዳትካፈል አግዶ መስተንገዶን አለባ ምክንያት በመሰረዝ 1 ሚሊዮንዶላር ቅጣትና 9 ኪሳራ እንድትከፍል ተወስኖባታል፤ አዘጋጅነቱን ለማግኘት ግብፅ ፤ጋና ፤አልጄርያ፤ኬንያ፤ ዚምባቡዌ ፤ጋቦንና ሱዳን ፍላጎት አላቸው፡፡
ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ያለቅድመ ማጣርያ ወደ ውድድሩ የሚያልፉ ቡድኖችን ለመለየት የምድብ ማጣርያ ብቻ የሚደረግ ይሆናል፡፡ በምድብ ማጣርያው 52 ብሄራዊ ቡድኖች አራት አገራት በሚደለደሉባቸው 13 ምድቦች ተደልድለው የማለፍ እድላቸውን ይወስናሉ፡፡ ከየምድቦቹ በአንደኛ ደረጃ የሚያጠናቅቁት 13 ቡድኖች፤ ምርጥ ሁለተኛ ደረጃ ያገኙ ሁለት ቡድኖች ይሳተፋሉ፡፡ በማጣርያው እንዲሳተፍ የሚገደደው አዘጋጅ አገር   በማጣርያው በመሳተፍ የሚያገኘው ውጤት በወዳጅነት ጨዋታ ይለካበታል፡፡
በሌላ በኩል በ2018 እኤአ ራሽያ ለምታስተናግደው 21ኛው ዓለም ዋንጫ በአፍሪካ አህጉር የሚደረገው ማጣርያ 3 የጥሎ ማለፍ ማጣርያዎች እና አንድ የምድብ ውድድርን የሚያካትት ይሆናል፡፡ በአፍሪካ አህጉር ለዓለም ዋንጣው ለማለፍ በሚደረጉት የ3 ዙር የቅድመ ማጣርያ ምእራፎች ስኬታማ የሆኑት 20 ብሄራዊ ቡድኖች እያንዳንዳቸው አራት አገራት በሚገኙባቸው አምስት ምድቦች በመደልደል በምድብ ፉክክር ይኖራቸዋል፡፡ ምድቦቹን በመጀሪነት የሚያጠናቅቁት አምስት ብሄራዊ ቡድኖች በ21ኛው የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ተወካዮች ይሆናሉ፡፡
በ30ኛው አፍሪካ ዋንጫ
ኮከብ ተጨዋችና ምርጥ ጎል - ክርስትያን አትሱ ጋና
ኮከብ ግብ አግቢ -አንድሬ አየው ፔሌ ከጋና በ3 ጎሎች 2 ጎል የሆኑ ኳሶችን በማቀበል
ኮከብ ግብ ጠባቂ- ሲልቭያን ጎቦሁ ከኮትዲቯር
ኮከብ ስፖርታዊ ጨዋነት -የዲሞክትራቲክ ኮንጎ ቡድን
ምርጥ ቡድን
ግብ ጠባቂ
ሲልቪያን ጎቦሁ ከኮትዲቯር
ተከላካዮች
ሰርጂዬ ኦርዬ ከኮትዲቯር፤ አሪሰን አፉል ከጋና፤ አቢብ ኮሎ ቱሬ ከኮትዲቯር
አማካዮች
አንድሬ አየው ፔሌ ከጋና፤ ያያ ቱሬ ከኮትዲቯር፤ ማክስ አሌያን ጋርዴል ከኮትዲቯር፤ ያኒክ ቦላሴ ከዲሪኮንጎ፤ ጀርቪንሆ ከኮትዲቯር
አጥቂዎች
ክርስትያን አትሱ ከጋና እና ዊልፍሬድ ከኮትዲቯር


በ2015 የአፍሪካ ክለቦች ውድድሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት የቅድመ ማጣርያ ተሳትፏቸውን ከሜዳቸው ውጭ በሚደርጓቸው ጨዋታዎች ይጀምራሉ፡፡ ከ2 ሳምንት በኋላ  የሁለቱም ክለቦች የመልስ ጨዋታዎች የሚደረጉት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በክልል በሚገኘው የባህርዳር  ስታድዬም ይሆናል፡፡
ለ19ኛ ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታው ከሜዳው ውጭ የሚገናኘው ከአልጄርያው ክለብ ኤኤምሲ ኤል ኦልማ ጋር ነው፡፡ በ1936 እኤአ የተመሰረተው የአልጄርያው ክለብ ኤል ኦልማ 25ሺ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታድ ሜቮውድ ዙጋር የሚጫወት ይሆናል፡፡
ኤል ኦልማ በፈረንሳዊው ጁሊዬስ ስኮርሲ የሚሰለጥን ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ ብዙ ልምድ የሌለው እና በ2008 የአልጄርያ ሊግ ሻምፒዮን የነበረ ነው፡፡በስፍራው የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የህዝብ ግንኙነት ክፍል እንደገለፀው በጨዋታው ላይ ቁጥራቸው በዛ ያሉ ወጣቶች እና ለአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ እንግዳ የሆኑ ተጨዋቾች ለመጀመርያ ጊዜ የመሳተፍ እድል ማግኘታቸው አንድ ትልቅ እርምጃ ሆኗል፡፡ እነሱም  ሰልሃዲን ባርጌቾ፤አንዳርጋቸው ይላቅ፤ዘካርያስ ቱጂ፤ መሀሪ መና፤ዳዋ ሁጤሳን ናቸው፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኤኤምሲ ኤል ኦልማ በደርሶ መልስ ጨዋታዎች የሚያሸንፈው በመጀመርያ ዙር ማጣርያ ሊገናኝ የሚችለው በቅድመ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታ ከሴራልዮኑ ኢስት ኤንድ ላዮንስ ወይንም ከጋናው አሻንቲ ኮቶኮ አሸናፊ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደደቢት  ለ12ኛ ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ ይሳተፋል፡፡ በቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ዛሬ የሚገናኘው ከሲሸልሱ ክለብ ኮቴ ዴ ኦር ጋር ይሆናል፡፡ የሲሸልሱ ክለብ ኮቴ ዴ ኦር 2 ሺ ተመልካች የሚያስተናግድ ስታድዬም ያለው ሲሆን በ2014 በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ብቸኛውን የተሳትፎ ልምድ አስመዝግቧል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በላከው መግለጫ ወደ ሲሺየልስ ካመራው የደደቢት እግር ኳስ ክለብ 29 የልኡካን ቡድን አባላት መካካል በቪዛ ምክንያት አራት የውጭ ሃገር ተጨዋቾች ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡  የሲሺየልስ ኢሚግሬሽን ባላስልጣን እ.አ.አ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ ያዋለውንና በምእራብ አፍሪካ ሃገሮች ዜጎች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን የተደረገው ጥብቅ የጉዞ መመሪያ ባለመከበሩ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ የተገደዱት የክለቡ ተጨዋቾች ሱሊማና አቡ፣ሞሃመድ አዳሙ፣ሳሙኤል ሳኑሚ እና ጋብርኤልአህመድ ሹኢብ ናቸው፡፡ ከደደቢት እና ከኮት ዴኦር  የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን የሚያሸንፈው በመጀመርያ ዙር የኮንፌደሬሽን ካፕ ማጣርያ ከቡርኪናፋሶው አርሲ ቦቦ እና ከናይጄርያው ዋሪ ዎልቭስ አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡

የገጣሚ ለማ ክብረት የግጥም ስብስቦችን ያካተተው “የኔ ወፍ” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ፡፡ በፊት ሽፋኑ ላይ ቀይ እንቡጥ ጽጌረዳ የያዘው መፅሀፉ፤ 108 ያህል ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን የግጥሞቹ ጭብጥ በፍቅር፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ በ110 ገፆች የተቀነበበው መድበሉ፤ ዋጋው 40 ብር ነው፡፡
በሌላ በኩል በታምራት መቻል የተፃፈውና 73 ግጥሞችን የያዘው “እንደባቢሎኖች” የሚል የግጥም ስብስብ  ከትላንት ጀምሮ ለንባብ በቅቷል፡፡ ግጥሞቹ በፍቅር፣ በማህበራዊና ፍልስፍና ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ 75 ገፆች ያሉት  መፅሀፉ፤ በ35 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

የጥናት ጽሁፎችን አደባባይ ለማውጣት ትኩረት ተሰጥቷል

 የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ከተቋቋመ ከ30 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በነሐሴ ወር 1982 ዓ.ም ለንባብ የበቃችው “ብሌን” የሥነፅሁፍ መፅሔት ፤ ከ15 ዓመት የህትመት መቋረጥ በኋላ ሰሞኑን ታትማ ዳግም ለአንባብያን ቀረበች፡፡
የደራስያን ማህበር 50ኛ ዓመት ክብረበዓልን ምክንያት በማድረግ በሰኔ 2003 ዓ.ም የ“ብሌን” መፅሔት ልዩ ዕትም (ቁ.7) ለንባብ መብቃቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ መደበኛው የመፅሄቷ ዕትም ለዓመታት ሳይታተም ቀርቷል፡፡ ከማህበሩ የ30 ዓመት ጉዞ በኋላ መጽሄቷ ብቅ ስትል ለኢትዮጵያ ሥነፅሁፍ ዕድገት እንደ አንድ ብስራት ቆጥረን ነበር ያሉት የአሁኗ የ“ብሌን” ዕትም አርታኢዎች፤ መፅሔቷ “ቅፅ 1፣ ቁጥር 1” መባሏ ቢያንስ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ዕትም በየዓመቱ ይታተማል የሚል ተስፋን የሚያመላክት ቢሆንም በማህበሩ የ24 ዓመት ታሪክ ውስጥ ከ7 የበለጠ የ“ብሌን” እትም ሊታተም አልቻለም ብለዋል፡፡
ለመፅሄቷ መቋረጥ ተጠያቂው ሁላችንም ነን በማለትም አርታኢዎቹ ኋላፊነቱን ለሁሉም አከፋፍለዋል፡፡ “… በመጀመሪያ ደረጃ የኢደማን አመራር ይዘው የነበሩትን ሁሉ የሚመለከት ቢሆንም የችግሩ አድማስ ግን ሁላችንንም የሚያካትትና ሁላችንንም በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ የሚያስጠይቅ ነው፡፡” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
አዲሱ የደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ መፅሄቷ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ የጠንካራ ተሳታፊዎች እጦት፣ የህትመት በጀትና የደጋፊ ወገን እጥረት መፅሄቷ ወቅቷን ጠብቃ እንዳትወጣ ዋነኛ ተግዳሮቶቿ እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ የመፅሔቷ ዕትም ትኩረት የተደረገው በምርምር አምባው ተወስነው የነበሩ የጥናት ውጤቶችን ወደ “ብሌን” መድረክ በማምጣት አደባባይ ማውጣት ላይ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተደረጉ ጥናቶች ውስጥ ሶስቱ (የስንቅነሽ አጣለ፣ የቴዎድሮስ ገብሬና የአራጌ ይመር) ተመርጠው እንደቀረቡ ተገልጿል፡፡
“የዚህ ዓይነቱ ሙከራ ወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ብሌን በምርምርና በፈጠራ፣ በሂስና በንድፈ ሃሳብ መካከል ድልድይ ሆና እንድታገለግል ምኞታችን ነው” ብለዋል፤ አርታኢዎቹ፡፡
በ108 ገፆች የተቀነበበችው “ብሌን” መፅሄት፤ ከጥናትና ምርምር ፅሁፎች በተጨማሪ አጭር ልቦለድና ግጥሞችን ያካተተች ሲሆን በ50 ብር ለገበያ ቀርባለች፡፡ መፅሄቷ በዓመት ሁለት ጊዜ እየታተመች ለአንባቢያን እንደምትደርስም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ጥበብ

በቴዎድሮስ ፍቃዱ ተደርሶ የተዘጋጀውና በቴዎድሮስ ፍቃዱ ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “ወንድሜ ያዕቆብ” የተሰኘ ፊልም ባለፈው ማክሰኞ በአቤል ሲኒማ ተመርቋል፡፡ በአብዱሰላም ሀሰን ፕሮዱዩስ የተደረገው የ1፡45 ኮሜዲ ድራማ ዘውግ ፊልም፤ መቼቱን በአዲስ አበባና በወሎ ሃይቅ ከተማ ላይ ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የፊልሙ ታሪክ ከወሎ፣ ሃይቅ እስጢፋኖስ፣ የእህቱን ሞት መርዶ ሰምቶ ወደ አዲስ አበባ የመጣ ያዕቆብ የተባለ ወጣትን የህይወት ውጣ ውረድ የሚያስቃኝ ነው፡፡ በፊልሙ ላይ ከ150 በላይ ተዋንያን የተሳተፉ ሲሆን ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ)፣ መታሰቢያ ታደሰ፣ እንግዳሰው ሃብቱ፣ ተዘራ ለማ፣ ቴዎድሮስ ፍቃዱና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከ8 ወራት በላይ እንደፈጀም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኤርሚያስ መኮንን ድርሰት የሆነውን “አጋምና ቀጋ” የተሰኘ መፅሀፍ ዛሬ ከቀኑ 8፡30 ጀምሮ አራት ኪሎ በሚገኘው ድንቅ ሥራ ህንፃ ላይ እንደሚያስመርቅ “ቡክ ኮርነር” አስታወቀ፡፡ ከምርቃት ሥነስርዓቱ በተጨማሪ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ደራሲያንና አንባቢያን በመፅሀፉ ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የ“Tower in the sky” ደራሲ ህይወት ተፈራ እና የ“The Young Crusader” ደራሲ  ሰለሞን ኃይለማሪያም በመፃህፍቶቻቸው ላይ የሚፈርሙበት ሥነ-ስርዓት እንደሚካሂድ “ቡክ ኮርነር” በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የአገር ታሪክ፣ባህልና ቅርስ ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱና አርአያ የሆነ ተግባር ላከናወኑ ግለሰቦች ከትላንት በስቲያ  የአርአያ ሰው ሽልማት ተበረከተ፡፡ በ“ዝክረ ሊቃውንት የሥዕልና የቅርፃ ቅርፅ ፕሮሞሽን” በተዘጋጀው  የሽልማት ፕሮግራም፤ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር፤ የቱሪዝሙ አባት አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ፣ የፊደሉ ገበታ አባት ቀኛዝማች ተስፋ ገብረስላሴ እና የቅኔዋ ምሁር እመት ገላነሽ አዲስ የአርአያ ሰው ሽልማት ተሸልመዋል፡፡
አቶ ዓለሙ አጋና መምህር ዓለማየሁ ፋንታ በበገና፣ አቶ ዮሐንስ አፈወርቅ በዋሽንት፣ አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) እና አስናቀች ወርቁ ደግሞ በክራር ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡
የአገሪቱን ቅርስና ታሪክ በመሰብሰብና በመጠበቅ አርአያ የሆነ ተግባር ያከናወኑና የአገሪቱን ባህል በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ የባህል ምግብ አዳራሾችም ከዕለቱ የክብር እንግዶች ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡  ሽልማቱ “ባህሌ፣ ታሪኬና ቅርሴ ማንነቴ” በሚል መርህ የተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዛሬ የሚከበረውን የፍቅረኞች ቀን (Valentine’s day) የሚዘክር የስዕል አውደ ርዕይ ትላንት በሞርኒንግ ስታር ሞል የተከፈተ ሲሆን በአውደ ርዕዩ የሶስት ሰዓሊያን ስራዎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡ ስራዎቻቸውን ያቀረቡት ሰዓሊያን እያንዳንዳቸው የአስር ሺህ ብር ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡት የሥዕል ሥራዎች ንብረትነታቸው የፕሮግራሙ አዘጋጅ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ለፍቅረኞች ቀን በተዘጋጀው የስዕል አውደ ርዕይ ላይ ለመሳተፍ ከቀረቡ 50 ሠዓሊያን መካከል ሶስቱን የመረጡት ዳኞች እንደሆኑ  ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Page 5 of 13