Saturday, 07 February 2015 13:48

አዶት ሲኒማ ዛሬ ይመረቃል

በዓይነቱና በአደረጃጀቱ እጅግ ዘመናዊ እንደሆነ የተነገረለት 600 ተመልካቾችን የሚይዘው አዶት ሲኒማና ቴያትር አዳራሽ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የኪነጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት ዛሬ ይመረቃል፡፡ ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በሚገኘው አዶት ሕንፃ ላይ የተሰራው የሲኒማና ቴያትር አዳራሽ በዘመናዊ መሣሪያዎች የጥበብ ሥራዎችን ለተመልካች ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

ወላጆቻቸውን በኤችአይቪ ኤድስ ባጡ ህፃናት የተዘጋጁ የጥበብ ውጤቶች የሚታዩበት “ተስፋ ኪነጥበብና ሙዚቃ ጋር” የተሰኘ የኪነ ጥበብ ኤግዚቢሽን ነገ በ ‹አለ› ዲዛይንና የስነ ጥበብ ት/ቤት ግቢ ውስጥ ይከፈታል፡፡
የእስራኤል ኤምባሲ ከእስራኤሉ ሃዳስ ዩኒቨርሲቲ ኤንግልሃርድ፣ ከነፃ የጥበብ መንደር የአርቲስቶች ቡድንና ከአርቲስት ፎር ቻሪቲ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸው ወላጆቻቸውን በኤች አይቪ ኤድስ ያጡ ህፃናት ከመቶዎች በላይ ልዩ ልዩ የጥበብ ስራዎቻቸውን በኤግዚሽኑ ላይ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡
“ተስፋ ከጥበብና ሙዚቃ ጋር የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚህ ዝግጅት ላይ ህፃናቱ በተለያየ አይነት አቀራረብና አሳሳል የሳሏቸውን ስዕሎች እንደሚያቀርቡና ኤግዚቢሽኑም ለአንድ ሳምንት ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን ኤምባሲው የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡  

ግጥም በማሲንቆን ጨምሮ የተለያዩ የኪነጥበብ ዝግጅቶች የሚቀርቡበት ሁለተኛው “የዘመራ ምሽት” ዛሬ ማታ በባህር ዳር ካስትል ኩሪፍቱ ዋይን ሃውስ ውስጥ እንደሚካሄድ የፕሮግራሙ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምስ አያሌው ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ በምሽቱ 13 ግጥሞች በማሲንቆ፣ ክራር፣ ዋሽንትና ከበሮ ታጅበው እንዲሁም ከጀርባ በተዋንያን ደምቀው እንደሚቀርቡ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ በየግጥሞቹ መሃልም የጐጃም ባህላዊ ሰርግ ከሆማ ቆረጣ እስከ ብር አምባር በግጥምና በተውኔት እንደሚተወኑ ተናግረዋል፡፡ የኔልሰን ማንዴላ የጀግንነት ህይወት ላይ የሚያጠነጥን ግጥም እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

    በሌላ በኩል ቦሌ መሰናዶ ት/ቤት አካባቢ በሚገኘው አናት ህንፃ 4ኛ ፎቅ ላይ የተከፈተው ልዑል ሲኒማ ሰሞኑን ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የሲኒማ ቤቱ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል አበበ ገለፁ፡፡ 400 መቀመጫዎችና 60 የቪአይፒ ወንበሮች ያሉት ሲኒማ ቤቱ፤ ዘመናዊ ሳውንድ ሲስተም እንደተገጠመለትና ወንበር መርጠው ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር እንዳለው ባለቤቱ ተናግረዋል፡፡ ሲኒማ ቤቱ ሳምንቱን ሙሉ በቀን አራት ጊዜ ጥራታቸውን የጠበቁ የአማርኛ ፊልሞችን እንደሚያሳይና የራሱ  ካፌና ሬስቶራንት እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡

Saturday, 07 February 2015 13:43

ልቻል ወይስ ልድፈር?

          ጉሮሮዬን በቀዝቃዛ ቢራ ለማርጠብ ወደ አንድ ምሽት ክበብ ደጃፍ ስደርስ አፍታም አልፈጀብኝም። ደጃፉን አልፌ ወደ ውስጥ እንደዘለቅሁ አንዲት እንስት አቀንቃኝ በታዳሚው የጋለ ጭብጨባ ታጅባ ወደ መድረኩ እየተውረገረገች ስትወጣ ተመለከትኩ። የቤቱ ኮከብ ዘፋኝ ትመስላለች። በእርግጥም ኮከብ ነች፡፡ ማይኩን ጨብጣ ተስረቅራቂ ድምጿን ስትለቀው አጃኢብ ነው። ድምጿን ስታወጣ ግብግብ የለም፡፡ ዝም ብሎ መስረቅረቅ ብቻ …
ተሰጥዖን ሲያገኙ እንዲህ ነው፡፡ ተሰጥኦ ባለበት የትግል ዱካ ይሸሸጋል፡፡ ዶልፊን ውሃ ላይ ለመሰልጠን ክንፎቹን እና ጭራውን ዝግጁ ማድረግ ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡ ዝግጁ ሲሆን ይከናወንለታል፡፡ ልክ እንደ መተንፈስ፡፡ ጥረት እና ትግል ለተሰጥኦ ምኑም አይደሉም፡፡ እንስቷ ማቀንቀንን ስለወደደች ብቻ ሁሉም ነገር በቀና እየሄደላት ነው፡፡
አቀንቃኟን ትክ ብዬ ሳስተውላት ግን ግራ ሆነችብኝ፡፡ ድምጿ ወዲህ፣ ስሜቷ ወዲያ ሆኖ አጥበረበረኝ፡፡ ከፊቷ የሚነበበው ስሜት ድንዛዜ ነው፡፡ በስጋዋ ልግምና ላይ ተሰጥኦዋ ቢታከልበት ኖሮ መስረቅረቁን ውሃ በበላው ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ከተራበ ጆሮ አንጀት የሚጠጋ ውብ ዜማ ከለገመው ገላዋ ላይ ማስወንጨፏን ቀጥላለች።
ከየማዕዘናቱ የሚያስተጋባ፣ ባዶነትን ያረገዘ ቅላጼ አሁንም አሁንም እየወተወኝ ነው፤ ውትወታውን በጄ ማለት እንዳለብኝ ወሰንኩ፤ ስለ ውብ ቅላጼ …ስለ ለገመ ገላ … ስለ ዜመኛዋ ውስጠ ወይራነት … ላወጣ ላወርድ … ተነሳሳሁ፡
በእርግጥም ይህቺን ውብ ዜመኛ ከተጣባት ልግምና በስተጀርባ አንድ ጥላ አጥልቷል፡፡ ጥላው  ለመኖር መታዘዝ ነው፡፡ የታዘዘችውን ካልከወነች እህል ውሃ ያከትማል፡፡ ተሰጥኦዋ ብልፅግና እንደተጠየፈ ይኸው እንዳለች አለች፡፡ ከተሰጥኦዋ የተረፋት ጥሪት ቢኖር ማገልገል ብቻ ነው፡፡ ታዛዥነቷ በተሰጥኦዋ ጉያ ውስጥ ተሸሽጎ ጎለመሰ እና ቀናት ቀናትን ሲወልድ ለአይን የሚያጠግብ  ወደል ሆኖ ታያት፡፡ ለምሽት ክበቡ ማቀንቀን አሀዱ ስትል፣ ከሀሴት ጋር ጫጉላ ላይ ነበረች፡፡ ያኔ ታዛዥነቷን፣ አገልጋይነቷን ዞር ብላ የምታማትርበት አንገትን አልተቸረችም፡፡ ብታማትረውም ገና ከእቅፍ ያልወረደ ጨቅላ ስለነበረ ቁብ አትሰጠውም፡፡ ጥቂት አገልጋይነት ብዙ ደስታ ነበራት፡፡ በስኳር የተቀባ መራራ መድሃኒት፣ ስኳሩ እስከሚያልቅ መጣፈጡን ይቀጥላል፡፡ የስኳር መጠኑ ሲያልቅ፣ ለመራራው ጣዕም ቦታውን ያስረክባል፡፡ ስኳር አልቆባት ከመራራው ጋር እየተጋፈጠች ነው። ከንፈሬን መጠጥኩላት፡፡ አሁን ይህች አቀንቃኝ ለድፍረት ነው ለችሎታ እጅ ያጠራት?
“ምን ልታዘዝ?” የሚል የአስተናጋጅ ድምጽ፣ ለጥያቄው መልስ እንዳላፈላልግ ለጊዜውም ቢሆን ገታ አደረገኝ፤
የምጠጣው ቢራ ከጉሮሮዬ አልወርድ እያለ ቢታገለኝም፣ ለሞቅታ ብዙም ጊዜ አልፈጀሁም። ሞቅታዬ ግን ቅድም ብልጭ ያለብኝን ጥያቄ ማሸነፍ  አልተቻለውም፡፡ ከድፍረት እና ከተሰጥኦ ማን ያስከነዳል? በእርግጥም ይህቺ ውብ አቀንቃኝ ከድፍረት ጋር ዓይን እና ናጫ ባትሆን ኖሮ እንዲህ በቢራ ለሚነፍዘው ታዳሚ ከመባከን አልፋ ለሀገር ምድሩ በበቃች ነበር፡፡ የአቀንቃኟ ሁኔታ ከበቀቀኗ ታሪክ ጋር ተገጣጠመብኝ፡፡ በቀቀኗ በታጠረላት ሽቦ (ኬጅ) ውስጥ ሆና ወዲህ ወዲያ ትበራለች። መብረር ተሰጥኦ ቢሆንም ከሽቦ ወሰን በላይ ፈቀቅ ማለት አልቻለችም፡፡ ሰማይ እየገመሰች መብረር ተክና፣ ክንድ በማትሞላ አጥር ውስጥ መንከላወሷ ምቾት ስላልሰጣት፣ የአድኑኝ ጩኸት ማሰማቷን ቀጥላለች፡፡ በጩኸቱ ልቡ የተነካ ደግ ሰው ወደ ሽቦው ተጠግቶ በሩን ከፈተና ወደ ሰማይ ለቀቃት። የተወሰነ ርቀት እንደተጓዘ ግን በድጋሚ ጆሮው የበቀቀኗን የአድኑኝ ጩኸት ይሰማው ጀመረ። መለስ ብሎ ወደ ኬጁ ሲጠጋ በቀቀኗ ልክ እንደ በፊቱ ከኬጁ ውስጥ ሆና እየጮኸች ነው፡፡ አሁን ግን የኬጁ መዝጊያ ወለል ብሎ ተከፍቷል። በቀቀኗን መርዳት ባለመቻሉ እያዘነ ተለያት፡፡ በቀቀኗ ከኬጁ ውጪ ያለው ህይወት ከማያውቁት መልአክ ሆኖባታል፡፡ ተሰጥኦዋን በሽቦ አጥሩ ልክ ገድባ መኖርን መርጣለች፡፡ በሌላ ጐን ደግሞ ደፋር መሰሎቿ በየዳሩ እንዳሻቸው እየከነፉ ከምንጩ ውሀ እየተጐነጩ፣ ከመስክ ላይ ጥሬ እየለቀሙ የሚኖሩት ኑሮ አስቀንቷታል፡፡ መብረር የሚችሉት ይቅርና ገና የተጐነደሸ ክንፍ ያላቸው ጫጩት በቀቀኖች ሳይቀሩ ከእርሷ በተሻለ ደፍረው ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ ይዘላሉ፡፡ የመብረር ተሰጥኦዋ ከጫጩቶቹ እጅግ ቢልቅም ድፍረት ስላነሳት ከእነርሱ በተሻለ በአደባባይ ልትታይ አልቻለችም፡፡
የእንስቷን አቀንቃኝ ተሰጥኦ ለማየት የታደሉት በምሽት ክበቡ ቅጥር ግቢ ውስጥ የታደሙት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከቅጥር ግቢ ባሻገር ላለው ህዝብ ተሰጥኦዋ ባይተዋር ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ አላላውስ ብሎ ቀፍድዶ የያዛት አባዜ ምንድን ነው? መፅሐፍ ቅዱስ የትጉህ እጅ አለምን ይገዛል ይላል፡፡ ይህ አባባል ለደፋሮች ቦታ የለውም፡፡ ደፋሮችም ለአባባሉ ቁብ አይሰጡም፡፡ ከትጋት ይልቅ ለብልጠት ይባትታሉ። ባትተውም አይቀሩም፤ በመጨረሻ ሲያሸንፉ ይታያሉ፡፡ የቀዬው አድባር ልቡ የሚሸፍተው ለሚደፍሩ እንዲ ለሚችሉ አይደለም፡፡ ጥያቄው ደፋር እንድሆን ማን ያስተምረኝ ነው? መልስ የለም፤ ከራስ ጋር ሙግቱ ቀጥሏል፤ የጠየቅሁት ጥያቄ እንደ ገደል ማሚቱ ተመልሶ ይሰማኛል፡፡
እንስቷ አቀንቃኝ መድረኩን ለሌላ አቀንቃኝ ለቃ ወርዳለች፡፡ ቅድም ክፍት ቦታ በብዛት ይታየኝ ነበር፡፡ አሁን ግን መፈናፈኛ እስኪታጣ ሁሉም መቀመጫዎች በታዳሚዎች ተይዘዋል፡፡ ከእኔ ቅርብ ርቀት ያሉት ቦታዎች በታዋቂ ሰዎች ምርኮ ስር ወድቀዋል፡፡ ታዳሚው ውስጡን በቢራ፣ አይኑን በታዋቂ ሰዎቹ ፊት እያጠበ መዝናናቱን ተያይዞታል። ታዋቂዎቹም ከታዳሚው ያገኙት ከልክ ያለፈ እንክብካቤ ሙቀት ጨምሮላቸው ልባቸውን እንደ ተራራ ቆልለዋል፡፡
“የደፋሮች ሀገር” ብዬ ከብርጭቆ ውስጥ የቀረችውን እንጥፍጣፊ ቢራ ወደ ጉሮሮዬ ላኳት፡፡
እነዚህ ባለ ጉንድሽ ክንፍ ደፋሮች ከእንስቷ አቀንቃኝ ሲነፃፀሩ መብረር ቢሳናቸውም እየዘለሉ መራቅ ችለዋል፡፡ ለተሰጥኦ እጅ ቢያጥራቸውም ለድፍረቱ ግን አልተቸገሩም፡፡ ለድፍረታቸው ምስጋና ይግባው እና ሁሉንም ዘርፍ እንዳሰኛቸው አክሮባት ይሰሩበታል፡፡ ለነገሩ የሚጠብቅባቸውን ግብር ነው ለአውደ ርዕይ ያቀረቡት፡፡ ባለተሰጥኦዎች ተሟልተው ወደ አደባባይ እስኪወጡ ድረስ እጃቸውን አጣጥፈው ይቀመጡ ማለት ኢ-ምክናያታዊ ነው፡፡ “If you wait until you become perfect, you will wait forever” የሚለውን የፈረንጆቹን አባባል ከባለ ተሰጥኦዎቹ በተሻለ ደፋሮቹ ተረድተውታል። ባላቸው ጉንድሽድሽ ክንፍ ለመብረር ይሞክራሉ፡፡ ለሚያያቸው ሰው የሚበሩ ይመስላሉ፡፡ በመብረር ህግ ግን መሬት ለቀቁ እንጂ በረሩ አይባልም። ከእይታ ገሸሽ አሉ እንጂ አልጠፉም፡፡ የሀሳብ ትርምሱ ከቤቱ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወርውሮ አውጥቶኝ ነበር፡፡ አሁን ወደ ቤቱ ተመልሻለሁ፡፡
ቤቱ ውስጥ የማየው ትእይንት ምንም ሰላም ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ ሁሉም የሚጠጣው የሚዝናናው አንዱ አንዱን እየጠበቀ ነው፡፡ ክብር እና ሞገስ ለሞቅታ እንኳን እጅ መስጠት አልቻሉም፡፡
ኪሴን ስዳብሰው ሟሽሿል፡፡ ብዙ ሳልሟሟቋ የያዝኳቸው የብር ኖቶች ጭዳ መሆናቸው ሰላም አልሰጠኝም፡፡ የቀበሌ መዝናኛ ውል አለኝ፡፡ እንደ እናት ጓዳ ያለስስት የሚቃመሱበት፤ በጥቂት የብር ኖቶች በርከት ያሉ ባለ አረንጓዴ እና ቢጫ ቦኖዎችን እጅ በእጅ የሚቀባበሉበት፤ ቦኖዎችን ተገን አድርጐ የከርስን ውትወታ በነፃነት አደብ የሚያስገዙበት፡፡ ሰዓቱ ባይገፋ ቀሪ የስራዬን ምስ እኔም እንደ ወዳጆቼ እዚያው ለማግኘት እንደረደር ነበር፡፡ ይህ ግን እንዳይሆን ምሽቱ ነጉዷል፡፡ ክበቦቹ ደርግ ላወጀው ሰዓት እላፊ ቃል አባይ ላለመባል በታማኝነት የፀኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ገራገር የብዙሃን ማጀቶች፣ “ሶሻሊዝም” ትቶ ያለፋቸው የህዝባዊነት ዳናዎች፤ ለአይን ያዝ እንዳደረገ ፍጥምጥ ማለትን ያውቁበታል፡፡ በእርግጥም ተፈጣጥመዋል፡፡ በእዚህ ሰዓት ወዴትም መላወስ የሚበጅ አይደለም፡፡ አንዱን ይዤ አንዱን መጣሌን ቀጥያለሁ፤ ድንገት ከወለል ጋር የተሳሳመ የቢራ ጠርሙስ ከሰጠምኩበት የምናብ ንትርክ ጐትቶ አወጣኝ፡፡
ድፍረቱም ተሰጥኦውም ድብልቅልቅ ብለውብኝ ስምታታ ኖሬያለሁ፡፡ ልድፈር ወይስ ልቻል? አሁንም ጥያቄው አልተመለሰም፡፡
የፅድቁ መንገድ የትኛው ነው? የእንስቷ ወይስ የታዋቂ ሰዎቹ? የታዋቂ ሰዎቹን መንገድ ይሻለኛል ብል “የጭቦ ክህነት ይቅርብህ” የሚል ተግሳፅ አዘል ሀይለኛ ድምፅ በውስጤ ያስተጋባል ብዬ ፈራሁ፡፡
አይ የእንስቷን መንገድ ልከተል ብዬ ብደመድም “ባክህ ተሰጥኦ ለበቀቀኗም አልጠቀመ” እያለ የሚሳለቅብኝ መሰለኝ፤ ታዲያ ብችል ነው ብደፍር የሚሻለው፡፡
ላም እሳት ወልዳ አይነት ምርጫ ሆነብኝ፤ እንደምንም ጥሪት ቋጥሬ፣ የቢራ አምሮቴን ልቆርጥ ፈልጌ ካልጠበቅሁት የሃሳብ ጋጋታ ጋር ስፋለም አመሸሁ፡፡
የእንስቷ አቀንቃኝ ድምፅ ተመልሶ ተሰማኝ፡፡ ከቅድሙ በተዛነፈ ሁኔታ ለዘፈኑ የምትደረድራቸው ስንኞች ቤት የማይመቱ ስድ ንባቦች ሆነው ወደ ጆሮዬ ይንቆረቆራሉ፡፡ ተስረቅራቂ ድምጿን ከሞቅታ ጋር ስሰማው የጣር ድምፅ ሆኖ ውስጤን ሸነቆጠኝ። የበቀቀኗ የአድኑኝ ተማፅኖ በእንጉርጉሮ መልኩ የመጣ መሰለኝ፡፡ እባክሽ እህቴ ደፈር በይ፤ መቻል ለበቀቀኗም አልጠቀመ… ብዬ የሚከተለውን ስንኝ በመቋጠር ከቤቱ ውልቅ ብዬ ወጣሁ፡፡
ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
የቻለብሽ ቀርቶ የደፈረሽ በላ  

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 07 February 2015 13:42

ተጠየቅ

ባንድነት ተዛምዶ….ያንድነት ተቃርኖ
አንድም በዝማሬ ………አንድም በ’ንጉርጉሮ
አንድም በዝማዌ..አንድም በአንባጓሮ
አንደዜም በብርዱ ……አንደዜም በግለት
አንደዜም በዘፈን…….አንደዜም በማህሌት
እንዲህ እኛ ና ኔ…..አንድም ሆነን ሁለት
ቀናና ጠምዛዛ ………ትጉና ነባዙ
ሐዘንም ይባቤ…….ጥፍጥፍ ጐምዛዛ
እራስና ግርጌ
ግርጌና እራስጌ
አዲስ እና አሮጌ..
በምኞት ትካዜ ከገባን ምናኔ
እኮ እኛ ማነን
ማነኝ እኛ ና’ኔ?!


Published in የግጥም ጥግ

        አራት ገበሬዎች አክሱም ጽዮን ሊሳለሙ ሲመጡ ቀዬአቸው ላይ አንዲት ጠብታ ዝናብ እንኳን ሳይጥል አክሱም ግን ከባድ ዝናብ ጥሎ ይቆያቸዋል፡፡
ጠላ ቤት ገብተው ሲያወጉ አንደኛው “እንደው ይሄ መድኃኔዓለምስ !! እንዳ ማሪያም አክሱም ወተት የሆነ ዝናብ ጥሎ ሲያበቃ እኛ መሬት ላይ ጠብ የምትል ዝናብ ይከልክለን?” ብለው ሲያማርሩ ምህረይ ጆሮ ውስጥ ጨዋታው ይገባል፡፡ ምህረይ መለስ አድርገው “እና እንደ እናቱ እንዲያያችሁ ትፈልጋላችሁ እንዴ?” አሉ ይባላል፡፡
ባለፈው ሳምንት ጽሁፌ ማገባደጃ ላይ በቸር እንሰንብት ብለን እንደተለያየነው ይኸው በሰላም ቆይተን ለቀጣይ ክፍል ደርሰናልና ተመስገን ነው መቼስ ሌላ ምን ይባላል፡፡ የክፍል አንድ ጽሁፌ ላይ እንደገለጽኩላችሁ፣ የምህረይ ወልደ ዩሀንስ የህይወት ጉዞ እጅግ ፈታኝና መከራ የተቀላቀለበት፤ አሳዛኙ የህይወት እጣ ፈንታቸውን በጸጋ ተቀበለው ነገር ግን ከዚያ ክስተት በኋላ አብዛኛው ማህበረሰብ “እብደት” ብሎ የሚጠራው፣ የፍልስፍና ባለሙያዎች ደግሞ “ህሊናዊ ምጥቀትን ማረጋገጥ” የሚሉትን ዓለም መስርተው ለሶስት ዐስርት ዓመታት ዘልቀዋል፡፡
ህሊናዊ ምጥቀትን ማረጋገጥ ምን ማለት ነው? ቀላል የሚመስል ነገር ግን ጥልቅ የሆነ ሃሳብ ውስጥ ስዋኝ በአጋጣሚ ስለ ምህረይ ወልደዩሃንስ በተጻፈው መጽሀፍ ላይ የግል ምልከታውን በአጭሩ ያኖረ ሰው በግሌ አፈላልጌ አገኘሁት፡፡ አቶ ጎይቶም ገብሩ ይባላል፡፡ አክሱም ከተማ ተወልዶ ያደገ ሲሆን ምህረይ ወልደዩሃንስን ከልጅነት ጀምሮ ያውቃቸዋል። በፍልስፍና የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አግኝቷል፡፡ “ፍልስፍና ዘ ካህሊል ጅብራን” የሚል መጽሀፍ በትግርኛ ተርጉሞ ለአንባቢያን እንዳደረሰ ነግሮኛል፡፡ ህሊናዊ ምጥቀትን ማረጋገጥ ምን ማለት ነው ? እንዴት ይረጋገጣል? ከፍልስፍና አንጻር እንዴት ይታያል? ከምህረይ ወልደዩሃንስ ህይወት ጋር የሚያገናኘው ነገር ይኖር ይሆን? የሚሉ እና ሌሎች ጥያቄዎችንም በቃለ መጠይቅ መልክ አቅርቤለት ነበር፡፡ የሰጠኝን ምላሽ ለጽሁፍ በሚመች መልክ አቅርቤዋለሁ፡፡
እብደት የተለያዩ መገለጫዎች ሊኖሩት ይችላሉ ይላሉ አቶ ጎይቶም፡፡ ከፍልስፍና አንጻር እብደት ማለት ምን ማለት ነው? ከምህረይ ወልደዩሀንስ የህይወት ታሪክ ጋር አያይዘው ቢያስረዱኝ? ብዬ ያቀረብኩላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ፤ በመሰረቱ እብደትን በሁለት መንገድ ከፍለን ልናየው እንችላለን። አንደኛው የህሊናዊ ወይም የመስተሀለይ  ምጥቀት የምንለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከህሊናዊ ዝቅጠት ጋር ልናያይዘው እንችላለን፡፡ የተለያዩ ፈላስፎች  ስለ እብደት የተለያዩ ነገሮችን ብለዋል፡፡ ለምሳሌ ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ እንዲህ ይላል፡- “በመጀመሪያ እብደት ነበር። እብደትም ከዘላለማዊነት ጋር ነበር፡፡ እብደትም ዘላለማዊነት ነው፡፡” ስለዚህም እብደት ሁሌም ያለና ከእኛ ጋር የሚኖር እንደሆነ ነው የሚነግረን፡፡ በተጨማሪም ኒቼ  “በቡድን ማበድ ወይም በቡድን ተደራጅተህ ማበድ በጣም የተለመደ ነገር ቢሆንም ግለሰባዊ እብደት ግን ብዙም የተለመደ አይደለም” ይላል፡፡ በመሆኑም ይሄ ወደ ግለሰባዊ አስተሳሳብ ወይም Individual way of being ወደ ሚለው ሃሳብ ይወስደናል፡፡ ይሄን ጉዳይ ከምህረይ ጋር ስናያይዘው ሁለት ነገሮችን መውሰድ እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው እርሳቸው በህይወታቸው ላይ በደረሰው ከባድ ሀዘንና መከራ ምክንያት ህሊናዊ ምጥቀት ያረጋገጡ ሰው ስለሆኑ  ወይም ከተለመደው አስተሳሰብና አካሄድ ወጣ ስላሉ፣ ህብረተሰቡ እብድ ብሎ ይጥራቸው እንጂ ህሊናዊ ምጥቀታቸውን ያረጋገጡ ሰው ነበሩ ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ሁለተኛው ነገር ግላዊ ህይወት ስለመምራት ፈላስፋዎች የተለያዩ ነገሮች የሚነግሩን በመሆኑ ከፍልስፍናዊ እይታ ጋር እያሰናሰልን ብንሄድ ጥሩ ነው፡፡ ፈላስፋዎች ይሄ ግላዊ ህይወትን ከሰዎች መንጋ ዓለም ጋር በማነጻጸር ይነግሩናል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ከመንጋ ውስጥ ማጣት የሚመርጡበት የራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኪርኪጋድ የተባለው ዴንማርካዊ ፈላስፋ ምን ይላል፤ “ሰዎች በቡድን ውስጥ ራሳቸውን ያጣሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት ለምሳሌ አንዳንድ እንስሳት ራሳቸውን ለመከላከል ሲያስቡ አፈር ይቆፍሩና ራሳቸውን አፈሩ ውስጥ ለመደበቅ ይጥራሉ፡፡ ልክ እንደ እንስሳቱ የሰው ልጅም ከመንጋው ለመራቅ በሚፈልግ ጊዜ ራሱን አፈር ውስጥ ይደብቃል እንደማለት ነው” ይለናል ኪርኪጋድ፡፡ ይህም ማለት ሰዎች አንድን አመለካከት በቡድን ሲይዙት ምንም ችግር ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን አንድን አመለካከት በግለሰብ ደረጃ ማራመድ ስትጀምር ችግር ይሆናል። ምክንያቱም በጋራ የሚታሰብ አመለካከት ካለ ለግላዊ ህይወት አስጊ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ግላዊ ህይወት ከዚህ ወጣ ያለ አስተሳሰብ ስለሆነ ነው፡፡
ማርቲን ሀይድጋርድ የተባለው ጀርመናዊ ፈላስፋ እንደሚነግረን ከሆነ ደግሞ “የሰው ልጆች ግላዊ አስተሳሰብን መቀዳጀት ካልቻሉ፣ ሳያስቡት ወደ የሰዎች መንጋ ዓለም ይፈጠፈጣሉ ይላል፡፡ አንድን ነገር ሌሎች እንዳዩት ማየት ስንጀምር ነው ፍጥፈጣው የሚከሰተው፡፡ እናም በነዚህ የሰዎች መንጋ ዓለም ራሳቸውን በማጣት፣ እንደ አንድ ተግባራዊ ስራ እንደሚሰራ ቁስ አካል ይታያሉ” ይላል፡፡ በሰዎች መንጋ አለም ውስጥ ራሳቸውን ያጡና አንድን የጥበብ ስራ ወይም አካሄድ ሌሎች እንዳዩትና ሌሎች ሂስ እንደሰጡበት እይታ ያዩታል። ስለዚህ የመንጋው ደስታ የእነርሱ ደስታ ይሆናል፡፡ የመንጋውን ሀዘን የእነርሱም ሀዘን አድርገው ያዩታል ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ግላዊ ህይወት ስንል ብዙ Existential Philosophers እንደ እነ ኒቼ፤ ኪርኪጋድ እና ከቅርቦቹም እንደ እነ ሀይድጋርድ እንደሚመርጡት “አንድ ሰው ግላዊ ህይወትን መምራት ካልቻለ በነጻነት ማሰብ ይሳነዋል” ብለው ስለሚያምኑ ነው። ሁለተኛው “የሰው ልጅ አንድ ነገር ከሌሎች ለየት ባለ መንገድ ለማየት ከፈለገ፣ ግላዊ ህይወቱን ነው መምረጥ ያለበት” ብለው ያምናሉ፡፡” ይህንን የፍልስፍና እይታ ወደ ምህረይ ስናመጣው ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ነው ጥያቄው፡፡ የምህረይ የእብደት ደረጃዎች አሉ፡፡ እርሳቸውን የሚያውቁ ብዙ ሰዎች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ መጀመሪያ ዝምተኛነት ያጠቃቸው ነበር -Silence የምንለው ማለት ነው። ከዚያም ብቸኝነት ያጠቃቸው ነበር - Solitude የምንለው ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ መጮህ፤ በነገሮች መሳቅና ማፏጨት የመሳሰሉትን ያደርጉ ነበር። እነዚህን ነገሮች ስናያቸው ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ለየት ብለው እንዲታዩ ያደረጓቸው መገለጫዎች ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ እነዚህ ድርጊቶች የህይወት ስቃይን ተጋፍጦ በማለፍ፣ ህይወትን እንደ ተራ ጨዋታ ነገር ቆጥሮ ኑሮን መቀጠል መቻል ሊባል ይችላል፡፡
ሌላው ምህረይ ስለ ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ነጻና ግላዊ በሆነ መልኩ በሽሙጥና በአሽሙር መልክ ሂስ ይሰጡ ነበር። ክላውድ ሳምነር የተባሉ በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ሰፊ ምርምር ያካሄዱ ሰው “የቅኔ ትምህርት ለኢትዮጵያ ፍልስፍና መሰረት ነው” ብለው ያምናሉ። (ምህረይ የቤተክህነት ትምህርት ጎጃም ድረስ ሄደው እንደተማሩ-የባለፈው ጽሁፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡) ለምን ቢባል “የቅኔ ትምህርት ተማሪዎች ነጻ በሆነና ግላዊ በሆነ መንገድ የማሰብና የመመራመር እድል ስለሚፈጥርላቸው፤ ቅኔ የፍልስፍና መነሻ ምንጭ ነው” ብለው ያምናሉ፡፡ እናም ምህረይ ከቅኔ ትምህርት ባገኙት እውቀት መነሻነት ግላዊ የሆነ አስተሳሰብ፤ እይታ እና ሂስ እንዲሰጡ አግዟቸዋል ሊባል ይችላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ብዙ ፈላስፋዎች እንደሚስማሙበት፤ የሰው ልጅ ግላዊ የሆነ አስተሳሰብ ማበጀት ካልቻለ በስተቀር (የቡድንን አመለካከትና አስተሳሰብ የሚደግም ከሆነ) አስተሳሰቡ ፍልስፍናዊ ነው ሊባል አይችልም፡፡
ምህረይ ቀን እንደ እብድ ሲጮሁ ውለው ሌሊት ደግሞ ቤ/ክ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፤ ይሄን እንዴት ትመለከተዋለህ ወይም ከምን የመነጨ ነው? ብዬም ጠይቄው ነበር፡፡
እንግዲህ ምህረይ ሁለት የተለያዩ ሰብእናዎች/ dual personalities/ እንደነበራቸው ከልጅነቴ ጀምሮ ሳስተውለው የነበረ ነገር ነው፡፡ እናም ምህረይ በሶስት መንግስታት ስርአት ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው ቀን ላይ በተለመደው አነጋገር እንደ እብድ ሆነው ህብረተሰቡን፤ ያለውን መንግስትን ሲወርፉ ውለው፣ ሌሊት ደግሞ ልክ እንደ ሌላው ካህን ሙሉ ሌሊት ቆመው የክህነት አገልግሎት ሲሰጡ ማደራቸው ሁለት የተለያዩ ሰብእናዎች ባለቤት እንደነበሩ አመላካች ነው፡፡
ምህረይ ሽሙጣቸው፤ ሂሳቸው ከባዶ የመነጨ አይደለም፡፡ በአስከፊው የአንበጣ ወረርሽኝ ምክንያት ቤተሰባቸው ለረሀብ በመጋለጡ፣ ቤተሰቤን አተርፋለሁ ብለው ስደትን መርጠው ወጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን ሶስት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን በአስከፊው የተስፋ ምድር ፍለጋ ጉዞ ምክንያት አጥተዋል፤ መሬታቸው ተዘርፏል፤ ተወስዷል፤ ፍርድ ቤት ሄደው መሬታቸውን ለማስመለስ ቢጠይቁም ምላሽ አላገኙም፡፡ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ተደራርበው በፈጠሩባቸው ጫና ምክንያት ዝምተኛነት፤ ብቸኝነትና ማፏጨትን ያዘወትሩ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በዚህም ምክንያት ራሳቸውን ለማጥፋት “ማይ ሹም” በሚባል ሃይቅ ውስጥ እስከ መግባት  የደረሱበት ሁኔታ እንደነበር መጽሀፉ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ በተቃራኒም ህይወትን እየወረፉ፤ እየተቹ፤ እያሄሱና እየቀለዱ መኖር እንደሚቻል ባለሙሉ ተስፋ እንደነበሩ መረዳት እንችላለን፡፡ እዚህ ላይ ፍሬድሪክ ኒቼ ያለውን መጠቀስ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ “ህይወትን ተስፋ ከመቁረጥና ካለመቁረጥ ባሻገር ማየት መቻል አለብን” ባይ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ከቻልን ብቁ ሰው ለመሆን አያዳግተንም ይላል፡፡ እናም ምህረይ ይህን ያረጋገጡ ሰው ነበሩ ለማለት እንደፍራለን፡፡ ነጻ ህሊናዊ አስተሳሰብ ለማረጋገጥ የቻሉ ነበሩ፡፡ ይህን ሁሉ መከራና ስቃይ ተቋቁመው ራሳቸውን ወይም ህይወታቸውን ማስቀጠል የቻሉ በጣም ቆራጥ ሰው እንደነበሩ ከህይወት ታሪካቸው ማረጋገጥ እንችላለን።
ሌላው መታለፍ የሌለበት ነገር ምህረይ ራሳቸውን እንደ አንድ ተራ ሰው ሳይሆን ልክ እንደ አንድ ታላቅ ንጉስ የሚመለከቱ ሰው ነበሩ፡፡ ራሳቸውን ሲጠሩ እንኳን  “ወልደዩሀንስ ንጉስ”  እያሉ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስለኛል የአስተሳሰብ፤ የመናገርና የአመለካከት ነጻነት ብቻ ሳይሆን የቦታ ነጻነት (Freedom of Space) ይፈልጉ የነበረው፡፡
እኚህ ሰው የሰዎችን የነፍስ ፍላጎት በቀላሉ የማንበብ እና የመረዳት ችሎታ ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ በፍጹም እንዲቀርቧቸው የማይፈልጓቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ምናልባትም የሰው ልጅ ደመነፍሳዊ ፍላጎትን በቀላሉ ማንበብ የሚችሉ ሰው ስለነበሩ ይመስለኛል። ፈላስፎቹ “Beastly Man ብለው የሚጠሩትን ግማሽ ሰው ግማሽ አውሬ ሰብእናን እንደማለት ነው። እናም የሰው አውሬ ባህሪውን በቀላሉ መረዳት የሚችሉ ዓይነት ሰው ነበሩ፡፡
እርሳቸው ህሊናዊ ምጥቀትን ያረጋገጡ እንደመሆናቸው ሌሎች እብዶችን (ወደ ህሊናዊ ዝቅጠት የተፈጠፈጡትን) ይጠየፉና ይሸሹ ነበር። በተለይ ሴት እብዶችን ሲፈሩ አይጣል ነበር፡፡ በመጽሀፉ ላይ ሴት እብዶችን ለምን እንደሚፈሩ አንድ ሰው ሲጠይቃቸው፤ “ኧረ ተወኝ ወንድሜ፤ ሴቶች ሲያብዱ ደግሞ የምራቸውን ነው፡፡ እንደኛ ለስለስ ያለ አይደለም፡፡ ያከሩታል፡፡” ብለውታል፡፡ በአሽሙሮቻቸው እንሰነባበት፡፡
ካለነበባችሁን
ምህረይ ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ጋር በምርጫ ሰሞን ያወጋሉ፡፡
ምህረይ፡ “እኛን ምረጡ እያላችሁ ለምንድነው የምታደርቁን? ለመሆኑ ከሌሎቹ እናንተ በምንድን ነው የምትሻሉት?”
የተቃዋሚው ፓርቲ አባል፡ “እኛ ምሁሮች ነን፡፡ ብዙ መጽሀፍቶችን አንብበናል፡፡”
ምህረይ፡ “ምን ዋጋ አለው ብዙ መጽሀፍ ማንበብ፡፡ በአግባቡ ካላነበባችሁን፡፡”
ሌላ እብድ
በአንድ ወቅት አክሱም ከተማ ውስጥ ድንጋይ የሚወራወር አዲስ እብድ መጣና ህዝበ አዳምን በድንጋይ ሲያራኩተው፣ ምህረይም እንደ ሌላው ሲሸሹ አንድ ሰው ያያቸውና፤ “ምህረይ እርስዎ እብድ ሆነው እንዴት እብድ ፈርተው ይሮጣሉ?” ብሎ ይጠይቃቸዋል።
ምህረይም ፈጠን ብለው“ ሁላችንም አብደን እንዳየነው እኛ ጨዋታ እንጂ ድንጋይስ አልወረወርንም ነበር፡፡ የዚህ ግን ለብቻው ነው ወንድሜ” ብለው ሩጫቸውን ቀጠሉ፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 07 February 2015 13:38

ወደ ነገ የፍቅር ወግ

ነገ፡-
ያራራቁንን መቶ ኪሎ ሜትሮች በፈጣኖቹ የመኪናው ጎማዎች ሽክርክሪት ስር እየጠቀለልኩ ወዳንቺ እከንፋለሁ፡፡ ናፍቆት ያሳበጠው ገላዬን ተሸክሜ እነዚያን የፎቅ ደረጃዎች መንታ መንታ እየተሻገርኩ በየእርምጃዬ ልክ ወዳንቺ እቀርባለሁ…….
የግንባሬን ላብ በክንዴ እየከላሁ፣ ያቀፍኩትን ስጦታ ለማበርከት እያመቻቸሁ፣ በኔና ባንቺ መካከል ያለውን ኮሪደር ጣጥሼ አልፋለሁ፡፡ የልቤን ፈጣን ምት ከቁብም ሳልቆጥር፣ ስለዛለ ገላዬ ላፍታም ሳላስብ፣ የውብ ገላሽን ማማርና የብቻ የጠረን ጣዕምሽን እያሰብኩ ድካሜን በናፍቆቴ አጣፋዋለሁ …….
እጣዬን የሚመስለኝን ቀዩን በርሽን በጉጉትና በጉጉት ደጋግሜ አንኳኳለሁ ……..
በሩን ቶሎ አትከፍቺም ……
በዚህም፣ ልቤ በጉጉት ልትፈርጥ፣ ቀልቤ በርሃብሽ ጠኔ ሊደባይ ምንም አይቀረውም፡፡ በናፍቆትሽና በሰቀቀንሽ ሲኦል ውስጥ ለድፍን ሁለት ደርዘን ሰከንዶች ተነክሬ ከተሰቃየሁ በኋላ በሩን ትከፍቻለሽ ……… !
ከዚያስ?
ከዚያ ……
“ውይ በናቲ ሞት! አንተው ነህ እንዴ?!” ትይኛለሽ - በልጅሽ እየማልሽ፣ ክንፉን ተሰብሮ እንዳልተሰበረ ለማሳየት ባየር ላይ እንደሚንደፋደፍ አሞራ ሆነሽ ……
ያኔ  …….. አይሻለሁ! …….
ታላቁ ቅላትሽ ከፍም እያምታታ፣ ከፀሃይ እያጥበረበረ  ይንቦገቦጋል ….. ታላላቅ ጡቶችሽ በለበስሺው ፒጃማ ውስጥ ሆነው ፋፍተው ይታያሉ  ….. ጠብደሎቹ ጭኖችሽ በተራመድሽ ቁጥር ዳሌሽን እያውረገረጉ ውስጤን በሙቀት ያጥለቀልቁታል  …… የሽንጥሽ ቅጥነትና ክበ’ት ምራቄን አድርቆ ጥምሽን ያረካልኝ ይመስል መቀነትሽን መሆን ያስመኘኛል ….. በዚህ መሃል አሎሎ አይኖችሽ የምስኪኖቹን አይኖቼን አከርካሪ በፍጥነት ሰባብረው የዕይታ አፅናፌን ከሽፋሽፍትሽ ዳርቻ በማንሳት በበርሽ ስር ምንጣፍ ላይ ይፈጠፍጡታል …..
ዕይታዬን እዚያው አርመጥምጬ ስረጋጋ፣ የአይኖቼን ብርሃን የእግሮችሽ ጣቶች ላይ አሳርፋለሁ ….. አቀላላቸው  ….. አረዛዘማቸው ….. አደራደራቸው …… አወቃቀራቸው …… ሁሉ ነገራቸው ውብ፣ ውቦች ……
“አ ……… አዎ ….. ደህና ዋልሽ ፀደይ! እ…. አብርሃም ነው እንዳደርስልሽ የላከኝ” እየተርበተበትኩ የያዝኩትን ያደራ ዕቃ አስረክባለሁ ……
“ውይ አብርሽዬ … የኔ ጌታ! እሱ ግን ደህና ነው? ወይኔ ሲያም…ር! ውይ የኔ ቆንጆ፣ ባለፈው ስላወራሁለት እኮ ነው ዛሬ የላከልኝ! ምስኪን አብርሽ! ቆይ አሁኑኑ እደውልለታለሁ ……. አንተ አትገባም ታድያ?” ትይኛለሽ ….
“አይ ….. እቸኩላለሁ፤ ደህና ዋይ” ብዬሽ ለስንብት አይኖቼን ወዳይኖችሽ እልካለሁ ….
አይኖችሽ እኔን አያዩም፤ ይልቅ ከአለቃዬና ከባልሽ የተላከልሽን ስጦታ በፍቅርና በናፍቆት ሰክረው ያደንቃሉ …… የቀኝ እጅሽ ውብ ጣቶች የስጦታውን ጀርባ ይደባብሳሉ ……. ውብ ጡቶችሽ የስጦታውን ደረት ከደረቶቻቸው ጋር ለጥፈው ለስጦታውና በስጦታው ይጨመቃሉ …… የግራ እጅሽ ጣቶችም እንደቀኞቹ ሁሉ የስጦታውን ቀሪ ጀርባ ለማቀፍ ሲሉ የያዙትን የበር መዝጊያ ይለቁታል …… ያ ደም መሳይ በራችሁም “ጥዝዝዝዝዝ …..” እያለ ሄዶ በበሩ መቃን ላይ በሚጠብቀው ሽንቁር ስር ምላሱን ይወትፋል ……
በሩ ይጋርድሻል፡፡
ያኔ ……
እኔ ……
በቀስታ የፎቁን ደረጃዎች መውረድ እጀምራለሁ።

Published in ጥበብ

      ባለፉት ጥቂት ዓመታት ስለ ሀገራችን ስነ-ጽሑፍ፣ ይበልጡንም ስለ ሀገራችን ግጥም መውደቅና መዋረድ ሙሾ አሟሽተን፣ ነጠላ ዘቅዝቀን፣ ድንኳን ጥለን ተላቅሰናል፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ ታምሟል እንጂ አልሞተም፡፡ ለግጥም የተወለዱ ችግኞቻችንን አረሞች ከነቀልንና ከኮተኮትን፣ ነገ ፍሬ እናያለን በማለት ለልቅሶ በተጣለው ድንኳን ውስጥ አበባ ነስንሰን፣ ዘንባባ ቀንጥሰን፣ የተስፋ ሽቶ ለማርከፍከፍ ሞክረናል፡፡
በተለይ ጋዜጦች፣ ይልቁንም አዲስ አድማስ ጋዜጣ በግጥም ዘውግ ላይ፣ ባልተልፈሰፈሰና የነገን አድማስ በናፈቀ ሁኔታ በጐ አስተዋጽኦ አድርጓል ቢባል ውሸት አይሆንም፡፡ “ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም”ና የኋላ እትሞችን ብንገላልጥ እውነቱን እናገኘዋለን፡፡ ምናልባትም አንዳንድ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሀን ለግብስብስ ጉዞ ምንጣፍ ሲያነጥፉ የተከላከልንበት ይኸው ጋዜጣ ነበር፡፡
አሁን አሁን ግን የዘመናችን ግጥሞች፣ በተለይ በቁጥር ጥቂት የማይባሉ ገጣሚያን ከብዙ አሰስ - ገሰስ ውስጥ እንደ ሰጐን አንገታቸውን አሠግገው፣ አንገት ከመድፋት ገላግለውናል፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ፣ አይኖቻችንን ጠራርገን ካየን፣ ከዚህ በፊት እያደነቅን ሰማይ ካደረስናቸው ገጣሚያን ጋር ሚዛን ላይ ብናስቀምጣቸው የላቀ አቅም ያላቸውን እናገኛለን፡፡ ለነገሩ የቱም ሥራ የሚለካው በየዘመኑ ዓውድ፣ ፍልስፍና፣ ማህበራዊ መዋቅር፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን መሠረት አድርጐ እንደሆነ የምንስተው አይመስለኝም፡፡ ጥበበኛ ሁሉ የሚለካው በየዘመኑ ነው፡፡ ይህንን ጠበቅ የሚያደርገው ደግሞ እንግሊዛዊው ገጣሚ ጆን ድራይደን ነው፡፡ በድራይደን እምነት፣ እያንዳንዱ ዘመን የየራሱ የላቀ አእምሮ ባለቤት (ጂኒዬስ) አለው፡፡ ቻርልስ ዲከንስ በዚህ ዘመን ሚዛን ቢለካ፣ ቀሽም የሚያሰኙት ብዙ ነገሮች እንዳሉት ፀሐፊው አስቀምጠዋል፡፡ እርግጥ አንዳንድ ገጣሚያንና ደራሲያን፣ የክፍለ ዘመናትን ድንበር ጥሰው፣ በሌሎች ዘመን ላይ ኮከብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንደ ኤሚሊ ዲከንሰን፣ በአፀደ ሥጋ በነበሩበት ዘመን ላይ ስማቸውና ሥራቸው ተዳፍኖ ከሞቱ በኋላ እንኳ ክፍለ ዘመን ይሻገራሉ፡፡
ወደ እኛ ጓዳ መለስ ስንል በኢትዮጵያ ሥነ - ጽሑፍ መድረክ ላይ ሥነ ጽሑፉን ለማገዝ ብቅ ካሉት ሰዎች ውስጥ አብደላ ዕዝራ አንዱ ነው። አብደላ የሚጣፍጥ ግጥማዊ ዜማ ያለው ብዕረኛ ነው፡፡ ምናልባትም ሳይዘረጥጥና ሳይቆነጥጥ በማባበል፣ችግኞችን ለማቅናት የመሞከር ዝንባሌ ያለው ፀሐፊ ነው ብል የሀቅን አጥር የዘለልኩ አይመስለኝም፡፡ በተለይ እንደ እኛ ሀገር ባለው የጋራ ባህል ትስስር ውስጥ ነገሮችን ከሥራ ጋር ከማያያዝ ይልቅ ተራና ሠፈራዊ ትርጉም በሚሰጥበት ሁኔታ ውስጥ አጐንብሶ ቅዝምዝሞችን በማሳለፍ ለውጥ ለማምጣት  መሞከር ቀላል አይደለምና ጥረቱ ትልቅ ነው፡፡
ለአብደላ ይህንን ያህል ቄጠማ ከጐዘጐዝኩ በኋላ የዘነጋቸው የመሠለኝንና ምናልባት ውለው አድረው በሀገሪቱ ሥነ ጽሑፍ ላይ አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ የምላቸውን ሥጋቶች ባነሳ ደስ ይለኛል። ይህንን ሥጋቴን አብደላን አግኝቼ ፊት ለፊት ብናወራው እመርጥ ነበር፡፡ ግን ደግሞ ሁላችንም ጊዜዎቻችን በእንጀራ ታሥረዋል፤ ሃሳቦቻችን በነገ ሩጫ ተወጥረዋልና በአንባቢያን ፊት ብናወራውስ? የሁለታችንም አደባባይ እንግዲህ ይኸው ጋዜጣ ነውና እነሆ፡-
ከሦስት ሳምንት በፊት ጥር 9 ቀን 2007 ዓ.ም የታተመውን ጋዜጣ ሳነብ፣ አንጋፋዎቹ፣ ወጣቶቹን ስለ መግፋታቸው የተነሣው ሃሳብ ምቾት አልሰጠኝም፡፡ እጅጉን ከነከነኝ፡፡ አብደላ ወጣቶቹን ይገፋሉ ብሎ የጠረጠራቸው እነማን ይሆኑ? ለመሆኑ እኛ ሀገር በግጥሙ ዘርፍ አንጋፋ የሚባሉት በሕይወት አሉ ወይ ብዬ ጠየቅሁኝ፡፡ ማን አለ? ገብሬ የለም፣ ደበበ ፀጋዬ፣ መንግስቱ ለማ፣ ዮሐንስ አድማሱ… የሉም፡፡ አንዳንዴ ኖረው በተወቃቀስን ሁሉ እላለሁ፡፡ መድረክ ላይ ሲያነቡ ባያቸው፣ ድምፃቸውን ብሠማ እናፍቃለሁ፡፡ ታዲያ አብደላ የሚገፉንን ሰዎች ከየት አመጣቸው ብዬ አሰብኩ። አሁን አንድ የቀረው ሰለሞን ዴሬሳ ይመስለኛል። እሱም በሰው ሀገር ስደተኛ ሆኖ ተለይቶናል፡፡ እንዲያውም አሁን አንጋፋ ሊባል የሚችለው ገጣሚ ነቢይ መኮንን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከዚያ ጐን ወንድዬ ዓሊ፡፡ አብደላ፤ “ወጣት ደራሲያን በዳበሳ እያደቡ የብርሃን ፈለግ አገኘን ብለው ምሁራን መከተል ይሻሉ፤ መገፍተራቸው ከአንጋፋው ራስ ወዳድነት ባሻገር አርቆ ያለማጤንም ህፀፅ ነው፡፡” ይላል፡፡
የቱ አንጋፋ የቱን ወጣት እንደገፈተረው አልገባኝም፡፡ ምናልባት የሌሉ ሰዎችን ሳናውቀው ወንጀለኛ እንዳናደርግ እፈራለሁ፡፡ የቀደሙትም እኮ የየአቅማቸውን ፅፈውልን አልፈዋል፡፡ ብዙዎቻችንም ልንበቅል የምንችለው በነርሱ ዘር ነው፡፡ እንደ እነ ኤስ.ቲ ኢሊየት፤ “በዳንቴ ግጥሞች ውስጥ በቅያለሁ”፣ እንደ ሩሲያዎቹ “ከጐግል ካፖርት ስር ተቀጥፌያለሁ” ማለት ባንችልም ቅሉ፣አንጋፋዎቹ ባለውለታዎቻችን መሆናቸውን አንድክድም፡፡
ባለፈው ሳምንት ቀድሞ ቅዳሜ በወጣው የአዲስ አድማስ እትም ላይ ደግሞ፣ አብደላ ምርጥ ብሎ የጠቀሳቸው ገጣሚያን ግራ አጋብተውኛል፡፡ መቸም ስለ ግጥምና ገጣሚያን ስናነሳ፣ አንዱ ከአንዱ የሚለይበትና የሚመጥቅበት የራሱ ሞገስና ግርማ እንዳለው ለአብደላ መንገር አያስፈልግም፡፡ የኤስኤች በርተንን “The Criticism of Poetry” ብቻ ያነበበ ሰው መልሱን በቀላሉ ያገኘዋል፡፡ ታዲያ አብደላ ለምን ዘነጋው? ይህ ዝንጋኤ የጐንዮሽ ጉዳት የለውም ወይ? ምናልባት አንዱ በሃሣብ ልቀት ቢበልጥ፤ ሌላው ከእርሱ የበለጠ የቋንቋ ልቀትና የምት፣ የተስማሞና የመሳሰሉት መመዘኛዎች ሃይል ከፍታ ሲዘመን የበለጠ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ይህ አይነቱ ዳኝነት በርተን፤ “The hasty and uncritical reader then plunges into his judgment I like this!” እንዳለው ይሆናል፡፡ አሊያም ዶ/ር አይ.ኤ. ሪቻርድስ “First impressions differ widely and notoriously unreliable” እንዳሉት የስሜታዊ አንባቢዎች ዳኝነት ሊሆንብን ነው፡፡ በርግጥ የግጥም መለኪያዎች እጅግ ብዙና ውስብሰብ መሆናቸውን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ሎውረንስ ፔረኔ እንደሚሉት፤ “…yet over a period of time the judgments of qualified readers tend to coalesce there comes to be more agreement than disagreement” ይላሉ፡፡ አንዳንዴ ግን ጥቂት የሚያከራክሩ አሉ፡፡ ለምሳሌ በውጭው ዓለም ለሼክስፒር ሶኔቶች ታላላቅ ምሁራን ሁሉ ሲያጨበጭቡ /ሳሙኤል ጆንሰንን ጨምሮ/ በጆንኪትስና በዶን፣ በቻውሰርና በወርድስወርዝ፣ በሼሊና በኤሌክሳንደር ፖፕ መካከል ግን ልዩነት ነበር፡፡ ግን ደግሞ እነዚህ የተጠቀሱት ገጣሚያን ከኪፕሊንግና ከሎንግፌሎው ከፍ ይላሉ የሚል ስምምነት አለ፡፡
ታዲያ እኛ ገጣሚያንን የምንፈርጅበት መለኪያ ምንድነው? አንዱን ከአንዱ ከፍና ዝቅ ስናደርግ የትኛው በምን ይበልጣል? በምን ያንሳል? የሚል ማሣያ ከሌለን የሚሻሻለው በምን ይሻሻል? አደረጃጀት፣ ቅጥንብር፣ ድምፀት፣ ዘይቤ፣ ተስማሞ - ሌላም ብዙ ነገሮች አሉ አይደል?
ይህንን ስል አብደላ ግድ የለውም ከሚል ዝንባሌ አይደለም፡፡ እንዳይዘነጋ ማሳሰብ ስላለብኝ እንጂ፡፡ አብደላ ለሀገራችን ስነጽሑፍ ከየትኛችንም ይልቅ ግድ እንደሚለው ከዚህ ቀደም የፃፋቸውን ሂሣዊ ዳሰሳዎች ማንበብ ብቻ በቂ ነው፡፡ ምናልባት አሁን ያለውን ሁኔታና የሰዎች ስነ ልቡናዊ አረዳድ አጢኖ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ግን ልብ ማለት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ እውነት ለመናገር፣ አሁን ያለው ወጣት ለመነቃቃትና ለመበረታታት ከቀድሞው የተሻለና የመተጋገዝ አዝማሚያ ያለው ነው፡፡
አቶ አብደላ ላይ ሌላም የመዘንጋት ዝንባሌ ያየሁ ይመስለኛል፡፡ የዛሬ ሁለት ሣምንት የብሩክታዊት ጐሣዬ “ጾመኛ ፍቅር” ላይ በሠራው ሂሣዊ ዳሰሳ ላይ ምናባችንን የሚያስጐዘጉዙ ወንድ ገጣሚያንን ስም ዝርዝር ከጠቀሰ በኋላ ከሴት ገጣሚያን አንድ ሁለቱ ስማቸው እንደተጠቀሰው ገጣሚያን እንዲያስደንቁን መናፈቁን ነግሮናል፡፡ አብደላ፤ እዚህ ቦታ፣ አሁንንና ወደፊትን ብቻ ያየ ይመስላል፡፡ ለመሆኑ ገጣሚ መቅደስ ጀንበሩና ሰዓሊና ገጣሚ ከበደች ተክለአብ በቀላሉ ይረሳሉ እንዴ? በምናብ ምጥቀት፣ በረጋ አደረጃጀት፣ በምትና ተስማሞ፣ በሸጋ ቃላት፣ ከሃሣብ ጋር ወጥተው በሚወርዱ ድምፀቶች ነፍሳችንን አስደንሰው፣ እምባችንን ጨምቀው አልረጩም እንዴ? የመቅደስ ጀንበሩን “ታቲሆያን” አንድ ሁለት ዐረፍተ ስንኞች እናስታውሳ፡-
ስህተት ናት - በእርግጥም ስህተት ናት
መዘመሯ ላጥቢያ ለንጋት ማዜሟ
ከደንቡ እንዳትወጣ ወግ እንዳይቀርባት
ድምጽዋን ማስደመኗ ቃሏን ማስለምለሟ
ስታውቀው ላይነጋ ብርሃን ላይታያት
በጩኸት ላይነጋ ጨለማው ዓለሟ፡፡
*    *    *
ወፎቹ ሲያዜሙ ሰምታ ሲዘምሩ
ማለዳ ተነስተው ደፋ ቀና ሲሉ
የንጋትን መምጣት በደስታ ሲያበስሩ
ምስጋና መግለጫ አንሶባቸው ቃሉ
ሲወድቁ ሲነሱ ሲከንፉ ሲበርሩ
ሲሯሯጡ እያየች ከዛፍ ዛፍ ሲዘሉ፡፡  
በነገራችን ላይ የሥነፅሁፍ ምሁሩ ብርሃኑ ገበየሁ በአማርኛ ስነግጥም መጽሐፉ፤ ገጣሚ መቅደስ ጀንበሩን እንዲህ ይላታል፤ “በዘመናዊው ሥነግጥም በሀለ - ሀለ የቤት ዓመታት ስልት እጅጉን ከተዋጣላቸው ወጣትና ዘመናዊ ገጣሚያን አንዷ ናት፡” ይሄ ብቻ አይደለም፣ የቤት አመታቱ፣ ስልትና ሙዚቃዊ ቃና ሸጋ እንደሆነ ይመሠክርላታል፡፡ ተምሳሌታዊ ፋይዳውንም በአድናቆት ከፍ አድርጐ ያሞካሻቸዋል፡፡ ““ታቲሆዬ” በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ የምትገኝ ዘማሪ ወፍ ነች፡፡ ግን ደግሞ በነፃነት ተምሳሌትነት በአፍሪካ የነፃነት ትግል ታላቅ ሚና የተጫወቱ ታላላቅ ሰዎችን ወክላ ተስላለች” በማለት ብርሃኑ የመቅደስ ጀንበሩን ሌላኛ ጥግ ያሰላዋል፡፡
እንግዲህ ይህ የተወሰነ ውበትና መልክ ነው፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከብሉይ መጻሕፍት ሲሶ ያህሉ በግጥም የተፃፈ መሆኑን የነገረ መለኮት አዋቂዎች ይነግሩናል፡፡ ይሁንና ከዚህ ሲሶ ውስጥ ግን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያህል የሚደነቅ የለም። ይህ መደነቅ ከየት መጣ ካልን፣ ዋነኛው ሚዛኑ ከመልዕክቱ ሌላ የዘይቤያዊ ቃላት አጠቃቀሙ ነው። በለዋጭ አነፃፃሪና ሰውኛ ዘይቤዎች ልብን እያዘለለ የሚያስደንስ ሃይልም አለው፡፡ ምናልባትም ብዕሩን ኮከብ ተጋጭቶ እሳት ይወልዳል ብንለው ይመጥን ይመስለኛል፡፡ እውነት ለመናገር አንዳንድ ቦታ ቃላቱ ጡት ሲጠባቡ እናያለን!
በሌላ በኩል ግጥሞችን በየዝርያቸው ማየትም ያስፈልገናል፡፡ ከተራኪ ግጥሞች እንደሌሪክ ዓይነት ባህሪ ጠብቀን፣ ሃሣቡ ጥልቅ ነው፤ ብንል ተሣሥተናል፡፡ ምክንያቱም በባህሪ ሁለቱም የተለያዩ ናቸውና፡፡ ጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን ስለ ከተሞች የፃፋቸውንስ ምን ልንል ነው? (ሃሣቡ ሲደንቅ ልንል?!)
ሃሣብ ብቻውን ግጥም አይደለም፡፡ ጥሩ መጣጥፍም ሊሆን ይችላል፡፡ ሃሣብ ከቡና ቤትና ከሌሎች ቦታዎችም መልቀም ይቻላል፡፡ ግን ግጥም ያ ብቻ አይደለም፡፡ በሰንደል እግር ቃላት ብናቆማቸው ወዲያው ይወድቃሉ፡፡
ፐረኔ፤ “በሃሳብ ብቻ ግጥም አይሆንም፤ መጣጥፍ ነው” እንዳሉት ሁሉ፤ ዴጋስ የተባሉ ፀሐፊ ደግሞ “You can’t make a poem with ideas you make it with words!” ብለዋል፡፡ የስነግጥም ምርምር መጽሐፍ የፃፉት ኤክስ ጄ. ኬኒዲም ይህንን ሃሳብ ይደግፉታል፡፡ “በዓለም ላይ እጅግ አስደማሚ የሆነው ሀሳብ እንኳ ግጥምን አይፈጥርም! ወይም ግጥም አይሆንም፡፡”  ይሁን እንጂ እኛ ሀገር በተለይ ከቅርብ ዓመታት በኋላ የመጣው ግጥም መመዘኛ ይህ እየሆነ ነው። ወደ ስህተት እየመራንም ያለው እርሱ ነው፡፡ ግጥም የብዙ አላባዊያን ቅንብር ነው፡፡ ጥሩ ሃሣብን እንደ አውሮፕላን ሞተር እንኳ ብንወስደው፣ ለመብረር ክንፍ ያስፈልገዋል፡፡ ቃላት ወሳኝ ናቸው፡፡ ዜማ፣ ስዕል፣ ምት፣ ማዕከላዊ ሃሣብን የማብሰልና የማጠንከር ጉዳይ ሁሉ ሊታይ ይገባል፡፡ አቶ አብደላ እዝራ ላይ ቅር ያሰኘኝም ይህ ነው፡፡ የሥነጽሁፍ ባለሙያዎችን ሲክብም ሆነ ሲንድ ምክንያት ቢሰጠን ደስ ይለኛል፡፡ የትኛው በየትኛው የውበት ሠፈር እንዳለ ለመለየት ያስችለናል፡፡ በተረፈ ግን ለሥነፅሁፋችን እድገት እየታተረ ነውና አድናቆቴን መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ መልካም ጊዜ፡፡

Published in ጥበብ

ከ100ሚ ብር በላይ ወጪ ተደርጐበታል

    የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት ዓለምና ትላልቅ (ሜትሮ ፖሊታንት) ከተሞች የሚጠቀሙበትን ኤክስ ፒ (XP) የተባለ የመጨረሻ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ትራንስሚተር ዛሬ በ11 ሰዓት በማዘጋጃ ቤት ግቢ በይፋ በማስመረቅ የ18 ሰዓት ቀጥታ ስርጭት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የአዲስ ቴሌቪዥን ስርጭት፣ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባና አካባቢዋ ፋይዳቸው የጎላ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የ18 ሰዓት ስርጭት እንደሚጀምር የኤጀንሲው የትምህርታዊና ዶክመንተሪ ዘርፍ ዳይሬክተርና የምረቃው ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ያረጋል ገልጸዋል፡፡
አቶ አበበ፣ በሂደት ወደ መካከለኛ ምስራቅ አገሮችና ለዚች አገር ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች ስርጭቱ እንዲዳረስ ይደረጋል ብለዋል፡፡
መረጃ የሚገኘው ከህዝብ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የምንሰራው ከህዝቡ ጋር ስለሆነ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ነን ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከሕዝቡ የሚያገኙትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እየተነተኑ ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው መረጃ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲው፣ የ18 ሰዓቱን ስርጭት ለመሸፈን በርካታ ዝግጅት በመደረጉ በኢኮኖሚ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች፣ ህብረተሰቡን እያዝናኑ የሚያስተምሩ ጉዳዮች እንደሚቀርቡ ጠቅሰው፣ በርካታ የአየር ሰዓት ለመዝናኛው ክፍል መሰጠቱን፣ በትምህርት ክፍል ዶክመንተሪና የምርመራ (ኢንቨስቲጌቲቭ) ጋዜጠኝነት ሥራ፣ እንዲሁም የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እንደሚቀርቡ፣ በማህበራዊ ዘርፍ (በትምህርት፣ በጤና፣ በወጣቶች፣ በሴቶች፣ በሕፃናት ..) ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ዘገባዎች ስራዎች እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
በኢኮኖሚው ዘርፍ ልማትን ማስተዋወቅና የከተማዋን ገጽታ መገንባት፣ … እንዲሁም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በምርመራ ጋዜጠኝነት ካሜራቸውን ደግነውና ብዕራቸውን አሹለው እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸው፣ ህዝቡ በየትኛውም ክፍል የሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን (ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ጉቦ፣ ሙሰኝነት፣ …) እንዲሁም ከህዝብ አፍና ከመንግስት ነጥቀው ለግል ጥቅምና ብልጽግና የሚያውሉ ሰዎችን እንዲያጋልጡ ተማፅነዋል፡፡
ፖለቲካ፣ በህዝብና በመንግስት መካከል በምርጫ የሚደረግ ስምምነት በመሆኑና የህዝብና የመንግስት ሚዲያ በመሆናቸው፣ ህዝብ የመረጠውን መንግስት እንደሚያገለግሉ ጠቅሰው የዚያን መንግስት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ … በማስተዋወቅ ህዝቡ እንዲፈጽማቸው ማድረግ ግዴታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህም ሲባል እኛ የምንሰራው ከገዢው ፓርቲ ጋር ብቻ ነው ማለት አይደለም ያሉት አቶ አበበ፤ አሁን የምንገኝበት ወቅት የምርጫ ቅስቀሳ የሚከናወንበት ጊዜ ስለሆነ፣ ማንኛውም ፓርቲ፣ ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ፖሊሲውን፣ ስትራቴጂውን፣ ሐሳቡን፣ … ማቅረብ ስለሚችል የማናስተናግድበት ምክንያት አይኖርም ብለዋል፡፡
አዲስ ቲቪ፣ ቀጥታ ስርጭት መጀመሩን ምክንያት በማድረግ፣ ከትናንት በስቲያ በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ፣ “የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ተቋማት በብሔራዊ መግባባት ስራ ላይ ያላቸው ፋይዳ” በሚል ርዕስ ሲምፖዚየም መካሄዱንና ከልዩ ልዩ የህዝብ አደረጃጀቶች  የተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን አቶ አበበ ያረጋል አስረድተዋል፡፡

Page 10 of 13