• “ሠማያዊ ፓርቲ የኔን መዋቅር ተጠቅሞ ነው እጩ ያስመዘገበው” አንድነት ፓርቲ  
  • -“እጩዎቻችንን ለማስመዝገብ ከቦርዱ አስፈፃሚዎች ተግዳሮት ገጥሞናል” ሰማያዊ ፓርቲ

      በቅርቡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአቶ ትዕግስቱ አወሉ እየተመራ ወደ ምርጫ እንዲገባ የወሰነለት እና በአቶ አበባው መሃሪ እንዲመራ የተወሰነው መኢአድ በምርጫው ለመወዳደር እጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ጠቁሟል፡፡
አንድት ፓርቲ ከ200 በላይ እጩዎች ማስመዝገቡን ያስታወቀ ሲሆን መኢአድ በበኩሉ፤ መረጃዎቹ ተጠናቅረው አልደረሱኝም ብሏል፡፡ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ፓርቲዎቹ ያስመዘገቧቸው እጩዎችን ብዛትን በተመለከተ ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም፡፡  
የአንድነት ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግስቱ አወሉ፤ ቦርዱ ፓርቲውን እንዲመሩ ከወሰነ ጊዜ አንስቶ ከቢሮ መረካከብ ጋር በተፈጠረው የጊዜ መጓተት ምክንያት በ5 ቀናት ውስጥ ብቻ በአዲስ አበባ ሃያ ሶስቱም የምርጫ ክልሎች ጨምሮ ከሱማሌ፣ ጋምቤላና ትግራይ በስተቀር በሌሎች ክልሎች 201 እጩዎችን ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
ለሌሎች ፓርቲዎች የተሠጠው 49 ቀን ሲሆን ለእነሱ 7 ቀን ብቻ እንደተሰጠና ፓርቲው በ5 ቀን ብቻ እጩዎቹን ለማስመዝገብ መገደዱ የፈለገውን ያህል እጩ ማቅረብ እንዳላስቻለው የጠቀሱት አቶ ትዕግስቱ፤ በማስመዝገብ ሂደቱ ፓርቲው በውዝግብ ውስጥ ማለፉ ተግዳሮት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎም አባላት ወደ ሠማያዊ ፓርቲ መቀላቀላቸው፣ ሠማያዊ ፓርቲ የኛን መዋቅር ተጠቅሞ እጩዎቹን ለማበራከት አስችሎታል ያሉት አቶ ትዕግስቱ፤ የአንድነትን አባላት ማስመዝገቡ የተገቢነት ጥያቄ ያስነሳል ነው ብለዋል፡፡ “ሠማያዊ ፓርቲ በተለይ በደቡብ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የአንድነት አባላትን አስመዝግቧል” ያሉት የአንድነት ሊ/መንበር፤ ይህም ፓርቲው ቀደም ሲል በአካባቢዎቹ መዋቅር እንዳልነበረውና አጋጣሚውን እንደተጠቀመ ያመለክታል ብለዋል፡፡ “የኛ ሰዎች ባይኖሩ ሠማያዊ ፓርቲ ምን ያስመዘግብ ነበር?” ሲሉ አቶ ትዕግስቱ ጠይቀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሠጡን የሠማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ እንኳን ከአንድነት ወደ ሠማያዊ የተቀላቀሉትን ቀርቶ የፓርቲውን ነባር አባላት እንኳ ለማስመዝገብ ችግር ገጥማቸው እንደነበር ጠቅሰው በተለይ ጐጃም ውስጥ ለፓርላማ 10 እጩዎችን እንዳናስመዘግብ ተደርገናል ብለዋል፡፡ ደቡብ እና ኦሮሚያ ላይ በግልጽ ሠማያዊ ፓርቲን የተቀላቀሉ የአንድነት አባላት መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ዮናታን፤ አዲስ አበባ ላይም ከ23 ቦታዎች በ4ቱ የአንድነት አባላት የነበሩት ይወዳደራሉ ብለዋል፡፡
ሠማያዊ ፓርቲ ከመነሻው 380 መቀመጫ ለማሸነፍ አልሞ 400 እጩዎችን እንደሚያቀርብ አረጋግጦ ወደ ምርጫው እንቅስቃሴ መግባቱን የጠቆሙት አቶ ዮናታን፤ የአንድነት አባላት የነበሩት በፖለቲካ ትግሉ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እየተመዘነ ለቦታዎቹ ታጭተው የነበሩ የሠማያዊ ፓርቲ አባላትን በመተካት እንዲገቡ ተደርጓል እንጂ ሠማያዊ የእጩ ችግር የለበትም ብለዋል፡፡ ለአንድነት የተመዘገቡ እጩዎች ሣይቀሩ ከአንድነት ለቀው ለሠማያዊ የመመዝገብ መብትም እንዳላቸው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል አቶ ዮናታን፤ የመኢአድ የምርጫ አስተባባሪ በበኩላቸው፤ ፓርቲው በተሰጠው አጭር ጊዜ ውስጥ እጩዎቹን ለማስመዝገብ መሞከሩን ጠቅሰው ምን ያህል እጩዎች ተቀባይነት አግኝተው ተመዘገቡ የሚለውን ለማወቅ ገና ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

       የኩዌት መንግስት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን በህገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ በማስገባት በቤት ሰራተኝነት ያስቀጥራሉ የተባሉ  12 ኢትዮጵያውያን ሴቶች በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እንዳስታወቀ አረብ ታይምስ ዘገበ፡፡
የሚኒስቴሩን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ 12 ሴቶችንና አንድ አሽከርካሪን በአባልነት ይዞ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ስራ ላይ እንደተሰማራ የተገለጸው ይህ ቡድን፣ በአንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት መሪነት በህገወጥ መንገድ ወደ ኩዌት የሚያስገባቸውን ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለአገሪቱ ዜጎችና ለሌሎች አገራት በቤት ሰራተኝነት ሲያስቀጥር ቆይቷል፡፡
የኩዌት የነዋሪዎች ጉዳይ ምርመራ ክፍል ባለስልጣናት፤ በድኑ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ላይ እንደተሰማራ ከታማኝ ምንጭ ያገኙትን መረጃ መሰረት በማድረግ ባካሄዱት ክትትል፣ የቡድኑን አባላት የህገወጥ የሰዎች ዝውውር በሚያከናውንበት ጀሊብ አል ሹዮክ የተባለ የአገሪቱ ክፍል በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የቡድኑ አባላት ከአገሪቱ የሰራተኞች ቢሮ ጋር የስራ ግንኙነት ያላቸውና በህጋዊነት የሚንቀሳቀሱ በማስመሰል በበርካታ የኩዌት ነዋሪዎች ላይ የማጭበርበር ድርጊት ሲፈጽሙ ነበር ብሏል፤ ዘገባው፡፡
በቁጥጥር ስር በዋሉት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር እየሰሩ እንደሚገኙም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Published in ዜና

አንድ ተጫራች 7 ሚሊዮን ዶላር አቅርቧል

የኢራን፣ የእስራኤልና የኩዌት ዜግነት ያላቸው ባለጸጎች፣ ቤተሰቦችና ተቋማት የቀድሞው የኢራቅ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን በስቅላት የተገደሉበትን ገመድ በከፍተኛ ገንዘብ በመግዛት የራሳቸው ለማድረግ የጦፈ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ተቀማጭነቱ በለንደን የሆነውን አል አራቢ አል ጃዲድ ድረገጽ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ግለሰቦቹ በቀድሞው የኢራቅ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሞዋፋቅ አል ሩባይ እጅ ውስጥ የሚገኘውን ይህን ገመድ የራሳቸው ለማድረግ እየተፎካከሩ ነው፡፡
ግለሰቡ በመኖሪያ ቤታቸው ከነሃስ በተሰራ የሳዳም ሃውልት አንገት ላይ ገመዱን አጥልቀው የሚያሳየውን ፎቶግራፍ ከሁለት አመታት በፊት ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ገመዱን በእጃቸው ለማስገባት ፍላጎት የሚያሳዩ ግለሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አንድ የወቅቱ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡
ገመዱን ለማግኘት በሚደረገው ፉክክር ከተሳተፉት መካከል፣ ሁለት የኩዌት ባለጸጎች፣ አንድ የኢራን የሃይማኖት ተቋም እና አንድ የእስራኤላውያን ሃብታሞች ቤተሰብ እንደሚገኝበት የጠቆመው ዘገባው፣ አንድ ተጫራች 7 ሚሊዮን ዶላር ማቅረቡን አክሎ ገልጧል፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ገመዱን ለማግኘት የተጀመረውን ጨረታ የተቃወሙ ሲሆን፣ ጨረታው የሚቀጥል ከሆነ ግን የሚገኘው ገንዘብ የአገሪቱን ህዝቦች ተጠቃሚ ለሚያደርግ ተግባር መዋል ይገባዋል ብለዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ብዙ ወጣቶች በምርጫ ድምጽ እንዲሰጡት ለማድረግ ነው
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን አባል የሆኑበት ወግ አጥባቂው ትሮይ ፓርቲ በቅርቡ በሚከናወነው ምርጫ ብዙ ድምጽ ለማግኘት በፌስቡክ ለሚያደርገው ቅስቀሳ በአመት ከ1 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ገንዘብ ወጪ እንደሚያደርግ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ፓርቲው ባለፈው አመት መስከረም ላይ ብቻ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እንዲወዱት ለማድረግ የከፈለውን 25 ሺህ ፓውንድ ጨምሮ፣ በወሩ በድምሩ 123ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ ለፌስቡክ ኩባንያ ገቢ ማድረጉን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፈው ህዳር ወር ፖለቲካዊ ይዘት ላለው ሌላ ድረገጽ 115 ሺህ ፓውንድ መክፈሉን አስታውቋል፡፡
ለፌስቡክ ይህንን ያህል ወጪ ማውጣቱን እንደ ትልቅ ኢንቨስትመንት እንደሚቆጥረው የገለጸው ትሮይ ፓርቲ፤ ገንዘቡን የሚያወጣው ቁጥራቸው የበዛ ወጣቶች በምርጫ ድምጻቸውን እንዲሰጡት በማሰብ እንደሆነ ቢገልጽም፣ የሚሳካለት አይመስልም ብሏል ዘገባው፡፡
በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅነትን በማትረፍ ረገድ፣ ብሪቴን ፈርስት የተባለው ፓርቲ ትሮይን በእጥፍ ያህል እንደሚበልጠው የጠቀሰው ዘገባው፣  ብሪቴን ፈርስት 650 ሺህ፣ ትሮይ ደግሞ 340 ሺህ ያህል የፌስቡክ ወዳጆች እንዳሏቸው ጨምሮ ገልጧል፡፡




Published in ከአለም ዙሪያ

*ውሳኔው ጨረቃ የማን ናት
በሚለው ጥያቄ ላይ ተጽዕኖ አለው ተብሏል

የአሜሪካ መንግስት፤ አገራት፣ የግል የህዋ ምርምር ተቋማትና ኩባንያዎች በጨረቃ ላይ የሚያከናውኗቸውን የንግድ ስራዎች በተመለከተ ቁጥጥር ማድረግ ሊጀምር እንደሆነ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
አሜሪካ ቁጥጥር ማድረግ እንደምትጀምር ማስታወቋ፣ ጨረቃ የማን ናት፣ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ወደ ጨረቃ መላክ የሚችሉትስ እነማን ናቸው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተጀመሩ ጥረቶችን አንድ እርምጃ ያራመደ ነው ተብሏል፡፡
የአገሪቱን ኩባንያዎች ጨምሮ በመስኩ የተሰማሩ የመላው አለም ኩባንያዎች መንኮራኩሮችን ወደ ጨረቃ መላክና የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን የሚችሉት ከአሜሪካ ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ ነው ያለው ዘገባው፤ ፍቃዱን የሚሰጠውም የአገሪቱ የፌዴራል አቪየሽን ባለስልጣን እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡
ባለስልጣኑ ያወጣው የቁጥጥር መመሪያ ኩባንያዎችና ተቋማት ወደ ጨረቃ ለሚያደርጉት ጉዞ ፈቃድ ከመስጠት በተጨማሪ፣ በጨረቃ ላይ የሚኖራቸውን ክልል የሚወስን ነው፡፡
አሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸደቀውንና ጨረቃ እና ሌሎች የህዋው አለም ቦታዎች በማንኛውም መንግስት ባለቤትነት ስር አይሆኑም የሚለውን ህግ እንደተቀበለች ያስታወሰው ዘገባው፣ ህጉ የግል ኩባንያዎች በጨረቃ ላይ እንዳያስቀምጡ ባይከለክልም፣ አሜሪካ ግን ይሄን አካሄድ ለመቆጣጠር መነሳቷን አስረድቷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

በ189 ዜጎች ላይም የሞት ቅጣት ጥላለች

   የቀድሞውን የግብጽ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በአመጽ ከስልጣን ለማውረድ ከአራት አመታት በፊት በተቀሰቀሰው አመጽ ተሳትፈዋል የተባሉ 230 የአገሪቱ አብዮተኞች ባለፈው ረዕቡ በካይሮ የእድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው  ቢቢሲ ዘገበ፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ታህሳስ ወር ላይ በካይሮው ታህሪር አደባባይ በተካሄደው አመጽ ከአገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል፣ የተለያዩ የመንግስት ህንጻዎችንና ተቋማትን በእሳት አቃጥለዋል የተባሉት እነዚሁ ተከሳሾች፣ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የቅጣት ውሳኔው እንደተላለፈባቸው ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ተከሳሾቹ ከእስራቱ በተጨማሪ በድምሩ 2ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በቅጣት መልክ እንዲከፍሉ በፍርድ ቤቱ ተውስኖባቸዋል፡፡
ቅጣቱ ከተላለፈባቸው ግለሰቦች መካከል በችሎቱ ተገኝቶ የፍርድ ውሳኔውን ያደመጠው ብቸኛ ተከሳሽ፣ አመጹን በማቀጣጠልና በመምራት ጉልህ ሚና እንደተጫወተ የሚነገርለት የ26 ዓመቱ አህመድ ዱማ፤ ዳኛው ክሱን በሚያነቡበት ወቅት በማጨብጨብና ጮክ ብሎ በመናገር፣ ተቃውሞውን ለማሰማት ሞክሯል ተብሏል፡፡
የተከሳሾቹ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ የተቃወሙ ሲሆን ዳኛው በተከሳሾቹና በጠበቆቻቸው ላይ ተጽዕኖ ሲፈጥሩ ነበር፣ የፍርድ ሂደቱ በአግባቡ አልተከናወነም፣ ውሳኔውም በአገሪቱ ታሪክ አስደንጋጭና የማይጠበቅ ነው ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተቃወመ ሲሆን፣ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይም በአገሪቱ የሚታየው የጅምላ እስራትና ቅጣት ከዲሞክራሲያዊ መርሆዎች ጋር የሚጋጭ ነው ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት በበኩ፤ ግብጽ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግዴታዎችን ስትጥስ ቆይታለች፤ የግብጽ ባለስልጣናት ይህንን ግዴታ ማክበርና ፍትሃዊ የፍርድ ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባቸዋል ብሏል፡፡
ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ባለፈው ሰኞም የእስላማዊ ቡድን አባላት ናቸው ተብለው በተጠረጠሩ 183 ግለሰቦች ላይ ባለፈው ሰኞ የሞት ፍርድ መበየናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት  ተሟጋች ተቋማት ፍርዱን መቃወማቸውን እንደገለጹ አመልክቷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

     “የአጭር ጊዜ ታሪክ ነው ያለው” እየተባለ በብዙዎች የሚነገርለት (በዚህ ባልስማማም)  የሀገራችን ኪነጥበብ በተለያዩ (በአብዛኛው ራስ ወለድ) በሆኑ ተግዳሮቶች እንደተያዘ “እንዲህ ነው” የማይሉት ጉዞውን እንደቀጠለ ነው፡፡ ብዙዎች “ኪነጥበባችን ካለው የአጭር ጊዜ ታሪክ አንጻር አሁን ያለበት ደረጃ ከፍተኛ የሚባል ነው” በማለት አድናቆታቸውን ሲገልጹ፣ ጥቂቶች ደግሞ “የደረሰበት ደረጃ የሚወደስ አይደለም፤ ይልቁንም እጅጉን ግልብ ነው” በማለት የቀዳሚዎቹን አስተያየት ይቃወማሉ፡፡
ወደ ጉዳዬ ከመግባቴ በፊት በሁለቱ አስተያየቶች ላይ ሊነሱ የሚገቡ አንዳንድ ጥያቄዎችን ልሰንዝር። “ኪነጥበባችን የአጭር ጊዜ ታሪክ ነው ያለው” የሚል መከራከሪያ ላይ የተመሰረተውን አስተያየት ላስቀድም፡፡ አያይዤም አልስማማበትም ያልኩትን ሀሳብ አስረዳለሁ፡፡
ኪነጥበብ ብዙ ዘሮችን/ዘውጎችን በስሩ የሚያቅፍ ጓዘ ብዙ መስክ ነው፡፡ በመሆኑም ኪነጥበብ ስንል ቢያንስ ሥዕልን፣ ቅርጻቅርጽን፣ ስነጽሑፍን (ግጥም፣ ልቦለድ፣ ተውኔት፣ ወግ…)፣ ሙዚቃን፣ ቴአትርን እና የፊልም ጥበብን እየጠራን ነው ማለት ነው፡፡ እነዚህ ጥበባት በሀገራችን ምን ያህል ረጅም ዘመናትን እንዳስቆጠሩ (ከፊልም ጥበብ በቀር) ለማወቅ ብዙ መድከም አያስፈልግም። ጥቂት ቀደምት ድርሳናትን ማገላበጡ ይበቃል፡፡
ሙዚቃው ብንል ሥዕሉ፣ ቅርጻቅርጹ ብንል ስነጽሑፉ… ምናልባትም ከብዙዎች ቀድሞ በሀገራችን ተጀምረዋል፡፡ ቀደምት አባቶች (እርፈቱንና ጽድቁን ይስጣቸው!) ጥበባቱን ከመጀመርም አልፈው ተራቀው አርቅቀዋቸዋል፡፡ ሊያውም ከማንም በፊት- ቀደም! ታዲያ “ካለው የአጭር ጊዜ ታሪክ አንጻር…” ማለት ምን ማለት ነው? እንደኔ ይህን ማለት በአጉል ቃል አባብቶ የማይገባ ይቅርታን ከመለመን ውጪ ሌላ አንድምታ አይኖረውም፡፡
ይህን ስል ግን “ኪነጥበባችን የትም አልደረሰም፤ አንዳችም መልካም ነገር የለውም፡፡” የሚሉትን እየወገንኩ አይደለም፡፡ ጉዞውንና ያለበትን ደረጃ የምር ፈትሾ፣ ገለባውንና ምርቱን፣ ትርፉንና ኪሳራውን በመለየት “እንደዚህ ነው፤ ወይም እዚህ ጋ ነው ያለው” ማለት እንደሚገባ ይሰማኛል፡፡ በደፈናው “እንዲህ ነው” ማለት ብቻውን በቂ ነው ብዬ አላምንምና፡፡ እርግጥ ነው ከምርቱ ይልቅ ገለባው እየበዛ አደከመን እንጂ (ቢያንስ በተወሰኑ ዘውጎች) መልካም ነገሮችን ማየታችን አልቀረም፡፡ መልካሙን ማውራት፣ መልካም ያሰራልና እሱንም መመስከር ይገባል፡፡
ያም ሆኖ ወደጎላው ነገር ስንመጣ የምናዝንበት ብዙ ነው፤ እጅግ ብዙ፡፡ በስነጽሑፉ ቢሉ በፊልሙ፣ በሙዚቃው ቢሉ በሌላውም እጅጉን የሚያሳዝኑና “ጥበባዊ ስራዎች ናቸው” ለማለት በፍጹም የምንቸገርባቸውን ስራዎች መድረኩና ገበያው እያስተናገደ ነው፡፡ እነዚህ ስራዎች ላይ በአብዛኛው የሚታየው አንድ የጋራ የሆነ ባህሪይም አንዳች ፍሬና ጥልቀት ማጣት ነው፡፡ ሀሳብን/ጭብጥን ቢሉ ስንክናዊ ውበትን (Aesthetic Value) ያጋቱ አይደሉም፤ ግልብ ናቸው፡፡
በየእለቱ ፊልሞች ይመረቃሉ፡፡ መጻሕፍት ይታተማሉ፡፡ ሙዚቃዎች ይለቀቃሉ፡፡ ሆኖም ግን ከጥቂት ስራዎች ውጪ አብዛኞቹ አንዳችም ፍሬ የማይገኝባቸው ገለባ ናቸው፡፡ ለዚህም (ምንም እንኳን ይሄ አንዳንዴ በቲፎዞ እና በእድል የሚወሰን ቢሆንም) ለወራት ሳይታይ የሚወርደው ፊልምና ቴአትር፣ ሳይሰማ የሚረሳው የዘመኑ ሙዚቃ፣ ገበያውን የሞላው የስነጽሑፍ ስራ ወዘተ… ዋቢ ነው፡፡ ይህንን ማለት ምናልባትም ጥቂቶችን ያስከፋ ይሆናል፡፡ ደግሞም ሁሉንም አንድ ላይ በጅምላ አጅሎ መተቸትም ሊመስል ይችላል፡፡ ፍሬዎቹን ለማግኘት ገለባውን ማንፈሱ የሚያድክመን ቢሆንም በየዘውጉ ሊመሰከርላቸው የሚገቡ ስራዎች አልፎ አልፎም ብቅ ማለታቸውን መካድ ቢያንስ ሞራላዊ አይደለም፡፡ እነሱን ባናገኝማ ምን ቀምሰን እናድር ነበር? በክረምትስ ቢሆን ፀሐይ እያሰለሰች ብልጭ ትል የለ!
ጉዳዬ የሀገራችን ኪነጥበብ ተግዳሮት ናቸው ከምላቸው ጉዳዮች መካከል ጥድፊያን እና ሆሆታን መዝዞ ጥቂት ማለት ነው፡፡ ሲመስለኝ ኪነጥበባችንን ገለባ ብዙ ካደረጉት ተግዳሮቶች መካከል ጥድፊያ እና ሆሆታ ሁለቱ ናቸው፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ በሀገራችን በተለይ አሁን አሁን እየተበጁ ያሉ ጥበባዊ ስራዎች እጅጉን በጥድፊያ የተሞሉ ናቸው፡፡ ቅኝታቸው ሩጫ ነው፤ “ረጋ ሰራሽ!”… የያዙትን ይዞ ወደ መድረክና ገበያ ለመውጣት ያለው ጥድፊያና ግፊያ ያህላል የለውም፡፡
የሰራሁት ምንድን ነው? ምን ይጎለዋል? ብሎ ለመፈተሽ፣ ለባለሙያ ለማሳየትና ክፍተቱን ለመሙላት የሚሆን ትዕግስቱም ሆነ ፍላጎቱ የለም። መሮጥ ብቻ፡፡ ገንዘቡ ካለ ደግሞ አለቀ። በአንድ ሳምንት ውስጥ ገበያ ላይ ይውላል፡፡ ሊያውም በሚያሳፍር ውሸት ተሽሞንሙኖ፡፡ “ይህንን ያህል በጀት ፈጅቶአል! ይህንን ያህል ዓመታት ተደክሞበታል!” ወዘተ ተብሎለት፡፡ እውነቱን ግን የምናውቅ እናውቀዋለን፡፡
የአንድ ጥበባዊ ስራ የመጀመሪያ ታዳሚም እንበለው ሐያሲ መሆን ያለበት ራሱ ባለቤቱ ነው፤ ከያኒው፡፡ እሱን ማርካት ያልቻለ ስራ ማንንም ሊያረካ አይችልም፡፡ ከያኒው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ስራው ውስጥ ይህንን መፈለግና ማረጋጋጥ አለበት፡፡ ለማንም ከማቅረቡ በፊት ራሱ የሰራውን ራሱ ቀምሶ ሊያጣጥመው ይገባል፡፡ ማንም ሴት ድግሷን ቀምሳ መጣፈጡን ሳታረጋግጥ ለእንግዶቿ አታቀርብም፡፡ ሳይቀምሱ ማቅረብ/መጋበዝ መሰደቢያን እንደማቀበል ነው፡፡
ከዚህም አልፎ በዘውጉ ላይ የተሻለ እውቀትና ምልከታው ላላቸው ባለሙያዎች ማሳየቱ የበለጠ ያተርፋል እንጂ አይጎዳም፡፡ ማንም በምንም ጉዳይ ምሉዕ አይደለም፡፡ በመሆኑም በየትኛውም ስራ ውስጥ (በራሱ ካልሆነ በቀር) ምልዑነት የለም፡፡ ምልዑነቱ አንጻራዊ በሆነ መልኩም ቢሆን የሚከሰተው ሌሎችም ባለሙያዎች እንደ አስፈላጊነቱ በሚያደርጉት አስተዋጽኦ ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህ አመለካከት ብዙዎችን ላያስማማ ይችላል። ነገር ግን ግምገማን የሚፈልጉና በባህሪያቸው እንደወረደ ቢቀርቡ የሚመረጡ ስራዎችን መለየቱ ይመስለኛል አንኳሩ ጉዳይ፡፡
ሌላው የሀገራችን ኪነጥበብ ተግዳሮት፣ ቀድሜ እንዳልኩት ሆሆታ ነው፡፡ ስክነት ማጣት፤ ተቀብሎ ማስተጋባት፤ በቅጡ ተገንዝቦ አለማስገንዘብ፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ፣ አንድ ስራ ለታዳሚ ሲቀርብ ሆሆታውና ውዳሴው ልክ የለውም፡፡ በእርግጥ ምንም ይሁን ምን አንድ ጥበባዊ ስራ ተሰርቶ ለህዝብ መቅረቡ በራሱ (የጥራትን ጉዳይ ትተን) ቢያንስ ከብዛት አንጻር  የሚጨምረው ነገር በመኖሩ “እንኳን ደህና መጣህ” ብሎ በክብር መቀበሉ ጉዳት የለውም፡፡ እየሆነ ያለው ግን እንደሱ አይደለም፡፡ ሳይመዝኑና ለምን? ሳይሉ የስራውን ትልቅነት በደቦ መመስከር፤ መቀባበል ነው፡፡ ስራውን በቅጡ ተረድቶ ከመዳኘት ይልቅ ሆሆታውን ማራገብ፡፡
የሚገርምው ነገር ታዲያ ከዚህ የሆሆታ ተዋናዮች መካከል ምናልባትም ዋነኞቹ በኪነጥበቡ ውስጥ የሚገኙ “ሙያተኞችም” ጭምር መሆናቸው ነው፡፡ አንድን ጥበባዊ ስራ፣ በሙያው የሌለ የሙያው አድናቂ ያልተገባ ደረጃ ቢሰጠው (መስጠቱ የተለመደ ነው) አስገራሚ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ታዳሚው ስራውን የሚዳኘው በአብዛኛው በስሜት ላይ ተመስርቶ እንዲሁም ከራሱ ገጠመኝ ጋር አያይዞ ነው፡፡ ስንክናዊ ውበትም በሉት ዘውጉ የግድ የሚላቸው ቴክኒኮች ወዘተ… አይገዱትም፡፡ ደግሞም ላያውቃቸው ይችላል፡፡ የግድ እንዲያውቃቸውም አይጠበቅም፡፡
በመስኩ ውስጥ የሚገኝ ባለሙያ ግን ከሆሆታው ተገልሎ ባለው አቅምም ቢሆን ስራውን ከተለያዩ አንጻሮች ሊፈትሽ ይገባል፡፡ ሲገባኝ ይህንን ማድረግ ሞራላዊም ሆነ ሙያዊ ግዴታው ነው፡፡ እየሆነ ያለው ግን እንደሱ አይደለም፡፡ ባለሙያውና ከሙያው ውጪ ያለውም በአንድ አብሮአል፡፡ የልዩነት መስመሩ ጠፍቶአል፡፡ ሆሆታው በጋራ ነው፡፡
ሒሱም ቢሆን ብዙም ራሱን ከሆሆታው አላገለለም፡፡ ሙያውና የሙያው ስነምግባር  የሚጠብቅበትን ከማድረግ ይልቅ ሆሆታው “ታላቅ ነው” ያለውን አጽድቆ ይመሰክራል፡፡ ጥቂት የምር የጥበቡ ተቆርቋሪዎች፣ የተገነዘቡትንና እውነት ነው ያሉትን በማጠየቂያ አስደግፈው በድፍረት ቢናገሩም ሰሚ የላቸውም፡፡ በሆሆታው ይታፈናሉ፡፡ ደግሞም ሆሆታው ቅጥልጥል ነው፡፡ ማቆሚያ የለውም፡፡ ለምን? እንዴት?… ማለትን የማያውቀው ሚዲያውም ሆሆታውን ተቀብሎ፣ አጉልቶና አድምቆ ወደ ህዝቡ ይለቀዋል፡፡ ብቻ ቲፎዞና አራጋቢ አይጥፋ ገለባው ሁሉ መልካም ስንዴ ይሰኛል፡፡ ማን “ሀግ” ብሎት!
እነዚህ ሁለት ተግዳሮቶች የሚያመጡት ጥፋት ይህንን ያህል ነው ተብሎ የሚመዘን አይደለም። በአጠቃላይ ጥበቡን “እግር ከወርች” ቀፍድደው ይዘውታል፡፡ ጥድፊያውም ሆነ ሆሆታው ሌላውን ትተን ቢያንስ ሁለት አካላትን በእጅጉ ይጎዳል- ታዳሚውንና በተለይ ደግሞ ራሱን ኪነጥበቡን፡፡
አንድ ኪነ ጥበባዊ ስራ ያለ ስክነትና እውቀት በጥድፊያ ተሰርቶ በመቅረቡ ሊደርስ የሚችልበትና የሚገባው ብቃት ላይ ሳይደርስ ይቀራል፡፡ በዚህም የጥበቡ ታዳሚ ገንዘቡን አውጥቶና ጊዜውን ሰውቶ የተሻለ እርካታ ማግኘት ሲገባው ገለባን እንዲጋበዝ ይገደዳል፡፡ ከሚያከብራቸው ባለሙያዎችም ሆነ ከሚወደው ሙያ ማግኘት ያለበትን ጥቅም ተነፍጎ ይጭበረበራል፡፡
የራሱ የኪነጥበቡ መጎዳት ደግሞ ይብሳል። በየዘመኑና ዘመኑ በሚፈጥርለት እድሎች (እውቀቶች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ ባለሙያዎች…) ማደግ ያለበትን ያህል ማደግ ሲኖርበት እድገቱን ይነፈጋል። ምክንያቱም በጥድፊያ የተሰራ ጥልቀት የለሽ ስራ ጥበቡን ባለበት እንዲረግጥ ያደርገዋል፡፡ ምናልባትም ጭራሽ ወደ ኋላ ይጎትተዋል፡፡  
በዚህ መንገድ የተፈበረከውን ስራ በማጀብ ያልተገባ መልክና ደረጃ የሚሰጠው ሆሆታም የሚያደርሰው ኪሳራ እንዲሁ ነው፡፡ ታዳሚን ያደናግራል፤ ያታልላልም፡፡ አሁንም ታዳሚው ማግኘት ያለበትን እውቀትና ተዝናኖት ያጣል፡፡
አሁንም በሆሆታው ከምንምና ከማንም በላይ እጅጉን የሚጎዳው ራሱ ኪነጥበቡ ነው፡፡ ሆሆታ አንድን ስራ በቅጡ በመመርመር የሚገባውን ቦታ ለመስጠት ፍላጎቱም ሆነ ትኩረቱ ስለሌለው ምርትና ገለባውን ማንፈሻው ከእጁ የለም፡፡ በዚህ መካከል ታላላቅ ጥበባዊ ስራዎች ቦታ የላቸውም፤ ወይም እነሱም በሆሆታው ውስጥ አብረው ታጅለው ያልፋሉ- ያላቸው የተለየ ዋጋ  ተከልሎ፡፡… ገለባውም የታላላቅ ስራዎችን ክብር ለብሶና ተሽሞንሙኖ ያልፋል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሂደት ውስጥ ሂደቱን ፈትሾ ምርቱንና ገለባውን የሚለይልን ሀቀኛ ሒስ የለም፡፡ በመሆኑም ቢያንስ ኪነጥበቡ የት ጋ ነው ያለው? የሚለውን እንኳን ማወቅ አንችልም፡፡
ተግዳሮቶቹ “ሀይ” ባይ አጥተው ኪነጥበባችንን ወዳሻቸው ከመሩት እነሆ ዓመታት አለፉ፡፡  ይኸውም ኪነጥበባችንን ገለባ ብዙና ደረጃ አልባ… እንዲሁም ትርምስምስ አድርጎታል፡፡   ባለሙያውም፣ ሒሱም፣ ሚዲያውም፣ ታዳሚውም… አውቀውትም ሆነ (ጥቂቶች ዓላማቸው በግል የሚያገኙት የማይገባ ጥቅም ነውና ከተግዳሮቶቹ ያተርፋሉ) ሳያውቁት የተግዳሮቶቹ ጠበቆች በመሆናቸው “እንወደዋለን! እናከብረዋለንም!” የሚሉትን ኪነጥበቡን እየጎዱት ነው፡፡ እስከመቼ የሚለውን ባናውቅም፡፡
መልካም ሰንበት!!

Published in ጥበብ

ተፈጥሮ ለጉልበት እንጂ ለፍቅር አታደላም
ቻርለስ ቡካውስኪ ከተፈጥሮ ጋር ታላቅ ቅራኔ ያለው ገጣሚ መስሎ ይሰማኛል፡፡ በአንድ ወቅት በገጣሚው ህይወት ላይ ያጠነጠነ ዶክመንተሪ መመልከቴ ትዝ ይለኛል፡፡ ዶክመንተሪው ውስጥ አንድ ቦታ ላይ ቡካውስኪ የሚያነባት ግጥሙ አለች። ቃል በቃል ትዝ ባትለኝም በጥቅሉ ግን አንድ ድመት አንዲት እርግብን የሚበላበትን አሰቃቂ እውነታ የሚገልፅ ነው፡፡
በድመቱ ክራንቻ ተይዛ ጥቂት ህይወት ብዙ ሞት በሚነበብባት ቅጽበት ውስጥ የተመለከተው ገጣሚ ወፏን እንደ ፍቅር፣ ድመቱን ደግሞ እንደ ተፈጥሮ አድርጐ መመሰሉን ይገልፃል፡፡
“ተፈጥሮ ጤናማ (Normal) አይደለም፤ እግዜር ጤናማ አይደለም” ይላል፡፡ ድመት ወፍን መመገቡ ለማንም የሚገርም ነገር ባይሆንም፣ ለገጣሚው ግን መግረም ሳይሆን ሰቅቆታል፡፡ ምክንያቱንም ሲናገር “ሌላው ሰው የማይገርመው ራሱን በተከሰተው ትዕይንት ውስጥ ተክቶ ስለማይመለከት ነው” ይላል።
እውነትም ደግሞ፤ ሰው ራሱን የተለየ አድርጐ ስለሚያስብ የአውሬ ተፈጥሮ፣ የመብላት እና መበላት ትያትር…የሰውን ልጅ እንደሚመለከተው አያስብም። ግን ሰውን የሚበላው ደግሞ ሌላ ሰው ነው፡፡
ቡካውስኪ ብቻ ሳይሆን እኔም ተፈጥሮን እንደ ጤናማ የማልመለከትበት ጊዜዎች ብዙ ናቸው። በተለይ የተፈጥሮ ህግ በጉልበት እንደሚሰራ በማገናዝብበት ጊዜያት ሁሉ፡፡
ተፈጥሮ ጤናማ እንዲሆን በጉልበት የሚሰራ ህጉ በፍትህ መስተካከል ነበረበት፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ድመቷም እንደ እርግቡ ጥሬ ትልቀም ማለቴ ይመስላል፡፡ ትርጉም የማይሰጥ ነገር ነው፡፡ ለድመቱ ክራንቻን የሰጠው ተፈጥሮ ለእርግቧ ደግሞ ክንፍን ሰጥቷታል፡፡
ተፈጥሮ፤ “ጉልበት ያለው ርትዕ አለው” በሚለው ህግ የሚሰራ ከሆነ “ህገ ልቦና” ተፈጥሮአዊ ያልሆነ ነገር ነው ማለት ይመስላል፡፡ በአምስቱ የተፈጥሮ ጣቶቻችን ላይ እንደተጨመረ ስድስተኛ ጣት፡፡
ገጣሚው ቡካውስኪ የእርግቧ መበላት ሲሰቀጥጠው፣ ራሱን እንደ ድመቱ ሳይሆን እንደ እርግቧ አድርጐ በመመሰሉ ምክንያት ነው፡፡ ጥፍር ሳይሆን ክንፍ የተሰጣቸው ሁሉ ወደ ተፈጥሮ ሳይሆን ወደ ፈጣሪ መቅረብ ነበረባቸው ብሎ ስለሚያምንም ሊሆን ይችላል፡፡ ተፈጥሮ የመጣው ከፈጣሪ ከሆነ፣ ድመትነት ከእርግብነት የበለጠ ወደ ፈጣሪ ይቀርባል፡፡ በይው በተፈጥሮ ህያው ሆኖ እንዲቆይ የሚፈለገው መሆኑ ነው፡፡ ተበይው የበይውን ህይወት ማስቀጠያ ነው፡፡
የተፈጥሮ ህግ በጉልበት ሲሰራ እንደዚህ ነው። ጉልበት ያለው ያሻውን ማድረግ መብቱ ነው፡፡ ድመቱ የርግቧን ክንፍ ነጭቶ ሊጫወትባት ይችላል፤ ወይንም ቸኩሎ ሊመገባት፡፡
የሰው ልጆችን በተመለከተ ቡካውስኪ የታየው እውነት፣ ከእርግብ እና ድመቱ ትራጀዲ የተለየ አይደለም፡፡ ሰውን ሌላ እንስሳ አይበላውም፡፡ ሰውን የሚበላው ሌላ ጉልበተኛ ሰው ነው፡፡ ህገ ልቦና (ስድስተኛዋ ጣት) የሰውን የእንስሳ ተፈጥሮ ልትለውጠው አትችልም፡፡ “ከእንስሳ የተለየህ ነህ” ብላ ማንነቱን ግን ልታድበሰብስለት ትሞክራለች። ሙከራዋንም ያምናል፡፡ ቢያምንም፤ እምነቱ ከእውነቱ አያስጥለውም፡፡
የሰው ተፈጥሮ ከእንስሳት የሚለየው መቀጠል መቻሉ ላይ ነው፡፡ ድመቱ ጥፍሮቹ ላይ ምንም መቀጠል አይችልም፡፡ ሰው ግን ጠመንጃ መቀጠል ይችላል፡፡ እርግቧ ክንፏ ላይ በተፈጥሮ ከተሰጣት ውጭ የምትጨምረው ነገር የላትም፡፡ ሰው ግን ሃይማኖትን ወይንም ጥበብን ይቀጥልበታል፡፡ መቀጠሉ ቱባ ተፈጥሮውን አይለውጠውም፡፡ ቱባ ተፈጥሮው ከአውሬ ጉልበተኝነት ብዙ አይለይም፡፡
ሰው መቀጠል ይችላል፡፡ በተፈጥሮው ላይ እምነት ይቀጥላል፡፡ በአምስቱ ጣቶቹ ላይ ስድሰተኛ ጣት፡፡ ተፈጥሮ “በፍቅር” ስለ መስራቱ የሚያሳምን ሃሳብ ሊያመነጭ ይችላል፡፡ ሃሳቡ ግን መልሶ ጉልበትን ለማደላደል ነው ጥቅሙ፡፡ በሃይማኖት ስም (ለፍቅር ሲባል) ጉልበትን በምእመናን ብዛት ያጠራቅማል። የእርግቧን ክንፍ ለብሶ የድመቱን ጥፍር ሲያወጣ ይስተዋላል፡፡ ፍቅርን በሀይል ለማስፈን ይጥራል፡፡ ጠመንጃም ያነግባል፡፡ በጠመንጃ ስም ፍትሀዊነትን ለማምጣት ይታገላል፡፡ ለማዳን ሲል ይገድላል። “ማንም የሰው ልጅ እንዳይሞት ጥቂቶች መሞት ይኖርባቸዋል” ብሎ ሰላምን በጉልበት ለማስከበር ይንቀሳቀሳል፡፡
ዋናው ነገር ግን አይለወጥም፡፡ ስድስተኛዋ ጣት አምስቶቹን የተፈጥሮ ጣቶች ተግባር ልትለውጥ አትችልም፡፡
በጦርነት አሸንፎ የገባ በንግግር አሸንፎ ለገባ ስልጣኑን ሊያስረክብ አይችልም፡፡ አምስቱ ጣቶች፣ ከበቀለ ጥቂት መቶ አመታት ላስቆጠረው ስድስተኛ ጣት ተፈጥሮአቸውን ሊያስገዙ አይችሉም። ስድስተኛዋ ጣት…ፍትህ ናት፡፡ ስድስተኛዋ ጣት ፍቅር ናት፡፡ ስድስተኛዋ ጣት ዴሞክራሲ ናት። ስድስተኛዋ ጣት ህገ - ልቦና ናት፡፡ መሆን የምንመኘውን ሁሉ ናት፡፡ መሆን የምንመኘው ከተፈጥሯችን ውጭ ነው።
ዲሞክራሲ የመናገር የመፃፍ መብት፣ በእናንተ ላይ እንዲደረግባችሁ የማትፈልጉትን በሌሎች አታድርጉ (እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ)፣ በህግ ፊት ሁሉም እኩል ነው…ስድስተኛዋ ጣት ድመቱ እርግቧን እንዳይበላ በእርግቦች የፀደቀች ህልም ትመስላለች፡፡ ወይንስ ድመቱ ላይ የሰው ጭንቅላት ሲጨመርበት እና እርግቧን ለመብላት የተሻለ የማስመሰያ ዘዴ ሲያክልበት የበቀለች ቅዥት ናት?
ተፈጥሮ ህገ - ልቦና የለውም፡፡ ደመነፍስ ብቻ ይመስላል፡፡ ሁሉም እንስሳ ሰውንም ጨምሮ የራሱን ህልውና ለማቆየት የመፍጨርጨሪያ አቅም ተሰጥቶታል፡፡ ግን በስተመጨረሻ እንዲያሸንፍ የሚሆነው ጉልበቱን በአቅሙ ላይ ማከል የቻለ ነው፡፡ በተፈጥሮ ቋንቋ መልካም እና እኩይ የለም፡፡ በህልውና መቆየት እና ዘሩን ማስቀጠል የቻለ አሸናፊ ነው፡፡ አሸናፊ ሁሉ ለተፈጥሮ የጨዋታ ህግ ፍትሀዊ ነው፡፡
ቡካውስኪ  “ተፈጥሮ ጤነኛ አይደለም” የሚለው ከስድስተኛዋ የህልም ጣቱ ባመነጨው እምነቱ ተመርቶ ነው፡፡ የክርስቶስ ትምህርት ስድስተኛዋን ጣት ትመስላለች፡፡ ከትምህርቱ የመነጨው ሃይማኖት ግን በህልውና መቆየት የቻለው (በስድስተኛው ሽፋን) ጉልበትን በተፈጥሮ አምስት ጣቶቹ ጨብጦ ነው፡፡
ተፈጥሮ ለጉልበት እንጂ ለእውነት አታደላም። ጉልበት ያለው እውነትም አለው፡፡ የጉልበተኝነት እውነት ለጉልበት አልባዎቹ ውሸት መሆኑ ተፈጥሮን አያገባትም፡፡ ጉልበት አልባውም ውሸትን ተጠቅሞ ጉልበት ማብቀል ከቻለ፣ አብቅሎም ሃያል ከሆነ ተፈጥሮ ትቀበለዋለች፡፡
የክርስቶስ ትምህርት ለድሆች እና አቅመ ቢሶች እንጂ ለሮማዊያኑ እውነት አልነበረም፡፡ ለሮማዎቹ፤ ደካማነት ማለት ሽንፈት፣ ደካማ ስለሆኑ ደግሞ ባርያ መሆናቸው የሚጠበቅ ነበር፡፡ ሮማ በተፈጥሮ ዲክሽነሪ የምትተረጐም መንግስት ነበረች፡፡ ክርስቲያኖች ጉልበት እያገኙ ሲመጡ ነገር ተገለበጠ፤ የሮማዊያኖቹ የቀድሞ እውነት አቅሙ ደከመ፡፡ ስለዚህ ከክርስቲያኖቹ ጋር መደባለቅ ነበረባቸው። የክርስቲያን እውነት በደጋፊ መብዛት ምክንያት ጉልበት ማግኘቱ አያጠራጥርም፡፡ ብዛት ራሱን የቻለ የጉልበት ምንጭ ነው፡፡ ጉልበት የሌለውን ተፈጥሮም ህልውናውን ታንኳስስበታለች፡፡
ተፈጥሮ ለጉልበት እንጂ ለፍቅር አታደላም። ተፈጥሮ ለጉልበት እንጂ ለውበት/ጥበብም አታደላም፡፡ እርግጥ ነው፤ ጥበብ ጉልበት አለው። ጉልበቱ ግን የጠመንጃን አፈሙዝ መቆልመም ስለማስቻሉ እጠራጠራለሁ፡፡ ጥበብም የስድስተኛዋ ጣት ውጤት ናት፡፡ ወይንም የስድስተኛዋ ጣት ናፍቆት፡፡ ጥበብም ስለ ፍቅር ይሰብካል፡፡ ስለ ፍትህ ጉድለት ይጮሃል፡፡ ተፈጥሮን በጥበብ ፈጠራ እንደገና ለማረቅ ይሞክራል፡፡ ግን ይህ ሙከራው ስድስተኛ ጣት ላበቀሉት ሁሉ ቢያማልላቸውም፣ ተፈጥሮን ግን ጥበብ በፈጠራው ማሸነፍ አይችልም። ዘማሪዋ ወፍ በዜማዋ ውበት ምክንያት በጭልፊት ከመጠለፍ መዳን አትችልም፡፡
ነብሩ እረኛው ዋሽንቱን ሲጫወት አርምሞ ውስጥ ገብቶ፣ ፈዞ ሲያዳምጥ እንደሚቆይ በተረት ተረት ሲነገር ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ ጉዳዩ አፈ ታሪክም ይሁን ተጨባጭ እውነት እኔ እንደ ምሳሌነቱ ተቀብዬዋለሁ፡፡
ባለዋሽንቱ ጥበበኛ ነው እንበል፡፡ ውበተኛ፡፡ ውበተኛም ሆነ ጥበበኛ፣ ነብሩ እያደነ ባለበት ሰአት ዋሽንቱን ቢጫወትለት እንደማይሰማው እርግጥ ነው፡፡ በእረፍቱ ሰአት ግን (አውሬው) ዋሽንት መስማት እና ውበት ውስጥ መሆን ሊወድ ይችላል። የመብል ሰአቱ ሲደርስ ግን ጥበበኛውን ከሌላው ታዳኝ ሳይመርጥ ውበቱን ገድሎ ይበላዋል፡፡ ጥበብ ጉልበት አለው፡፡ ሰውን ከተፈጥሮ የአውሬ ባህሪው ማጽዳት የሚችል ጉልበት ግን አይደለም፡፡
እኔም አሁን እያፃፍኩ ያለሁት በአምስቱ ጣቶቼ እስክሪብቶውን ጨብጬ፣ እውነቴን ግን ከስድስተኛው ጣት እያፈለቅሁ ነው፡፡ እንደ ቡካውስኪ እኔም ጉልበት (ተፈጥሮ) ጤነኛ ስላለመሆኑ አምናለሁ፡፡ ግን እምነቴ ተጨባጩን የተፈጥሮ ባህርይ ሲለውጥ ተመልክቼ አላውቅም፡፡ እምነቴ በተፈጥሮ ቀዳዳ ላይ እንደተጣፈ ባዕድ ቀለም ያለው ጨርቅ መስሎ ይሰማኛል፡፡ እምነቴ ውሀን ሽቅብ እንዲፈስ ማድረግ ሲችል አላየሁም፡፡
Nature VS Nurture – Nature ways wins የሚሉት ወደው አይመስለኝም፡፡ ሳይንቲስቶች በሰው ልጅ ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥን ሲያመጡ ማየት የቻልነው ተፈጥሮ ላይ ስለሚያተኩሩ ብቻ ነው፡፡ ሳይንስ ህገ ልቦናን አያጠናም፡፡ ሳይንስ መልካም እና እኩይን ሳይሆን ተጨባጩን እውነታ ነው የሚመረምረው፡፡ መርምሮ የሚያቀርበው ፈጠራ ደግሞ ከተፈጥሮ ባህርይ የተቀዳ በመሆኑ እውነተኛውን ተፈጥሮ ማገልገሉ አይካድም፡፡ እውነተኛው ተፈጥሮ:- ጉልበት…ፍትህ ነው፣ ጉልበት ህይወት ነው፣ ፍቅርን ጉልበት ይገዛዋል (ጉልበት ያለው ነው የሚፈቀረው)…የሚል ይመስለኛል፡፡ ከመሰለኝ ደግሞ ነው!    

Published in ጥበብ

በከተማ አድማሱ የተፃፈውና በሥነ - አዕምሮ ጤና ላይ የሚያተኩረው “ስነ-አዕምሮ” የተሰኘ መፅሐፍ ባለፈው ሳምንት ለንባብ በቅቷል፡፡ ለበጎ ስሜትና ለጤናማ አዕምሮ ባለቤትነት እንደ መመሪያ ያገለግላል የተባለው መፅሀፉ፤ የጭንቀትና የድብርትን እንቆቅልሽ የሚፈታና የአዕምሮ ጤና እውቀትን የሚያጎናጽፍ በመሆኑ ሁሉም ሊያነበው እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ በአምስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ340 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ70 ብር ለገበያ መቅረቡም ታውቋል፡፡

በገጣሚ በቀለ ፍቃዱ (ነሁቸር) የተፃፉ የግጥም ስብስቦችን የያዘ “ፍንጃል ወግ” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መድበሉ ከመቶ በላይ ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን ግጥሞቹ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም  በፍቅር ዙሪያ ያጠነጥናሉ ተብሏል፡፡ በ130 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤በ19 ብር ከ50 ሳንቲም ለገበያ የቀረበ ሲሆን በቅርቡም “እንዶድ፣ ዘመቻና ዘመን” የተሰኘ ረጅም ልብ ወለድ ለንባብ እንደሚያበቃ ገጣሚው ገልጿል፡፡