የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ለአገሪቷና ለቢዝነስ ሰዎች ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ የታመነበትን “የኢትዮጵያ ቢዝነስ ተቋማት ሞዴል የሥነ ምግባር መመሪያ” ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅቶ አስመረቀ፡፡
ባለፈው ሳምንት በሒልተን ሆቴል በፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የተመረቀው የሥነ ምግባር መመሪያ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በንግድና አገልግሎት፣ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተዘጋጀ ሲሆን የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እንደየሥራቸው ባህርይ በመተርጐም ሥራ ላይ የሚያውሉት እንደሆነ ታውቋል፡፡
አንድ የንግድ ድርጅት ከሠራተኞቹ፣ ከደንበኞቹ፣ ከባለአክሲዮኖቹ፣ በሥራው አጋጣሚ ከሚገናኛቸው ተቋማት፣ ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አባላት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሊኖረው የሚገባው ግንኙነት ሕጋዊ መሠረት ያለውና በሥነ ምግባር መርህ የተደገፈ ሊሆን እንደሚገባ የጠቀሱት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ በዚህ መልክ ታስቦበትና ታቅዶበት ካልተሠራ በስተቀር ለተወሰነ ጊዜ አትራፊ መስሎ ቢታይም መጨረሻው ግን ውድቀት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተር፤ የግሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ በአግባቡ እንዲሠራና ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ዶ/ር ሙላቱ፣ የንግዱ ዘርፍ አባላትም በግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ተአማኒነት እንዲሁም በማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ፅኑ ፍላጐት እንዳለው ገልፀዋል፡፡
ማንኛውም ሙያ የራሱ ሥነ ምግባር አለው፡፡ በተለይም የቢዝነስ ዘርፍ በርካታ ፍላጐቶችና ስሜቶች የሚንፀባረቁበት በመሆኑ የቢዝነስ ሥነ ምግባር ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ይመለከታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የሥነ ምግባር መመሪያው መዘጋጀቱ በራሱ አንድ ትልቅ ሥራ ሆኖ በመመሪያው ውስጥ የተጠቀሱ ቁምነገሮችን እያንዳንዱ የንግድ ተቋም ተቀብሎ በተግባር ቢተረጉማቸው ሀገራዊ ፋይዳቸው እጅግ ትልቅ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ትስስር እየፈጠረ ስለሆነ በንግዱ ማኅበረሰብ የሚተገበር የቢዝነስ ሥነ ምግባር ማዘጋጀት እንዳስፈለገ የጠቀሱት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ፤ የሥነ ምግባር መመሪያው በራሱ የሚተማመን ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ከማስቻሉም በላይ ሙስናን እንዲፀየፍና እንዲዋጋው ስለሚያግዘው በሥነ ምግባር የታነፀ የንግድ አሠራር እንዲፈጠር ጉልበት ይሆነዋል ብለዋል፡፡
የቢዝነስ ተቋማት ሞዴል የሥነ ምግባር መመሪያው ሁለት ዓላማ ይዞ ነው የተዘጋጀው፡፡ የአገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር እየተወዳጀና እየተቆራኘ ስለሆነ ሰፊ ጥያቄና ከፍተኛ ዕድልም ይዞ እየመጣ ነው ያሉት የንግድ ም/ቤቱ ም/ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ፣ የዓለም ኢኮኖሚ በከፍተኛ ጥንቃቄና ሥነ ምግባር የሚንቀሳቀስ ስለሆነ ጥያቄውን በትክክል መመለስ ከቻልን ተጠቃሚ እንሆናለን ብዋል፡፡
“ንግድና ኢንቨስትመንት ለማኅበረሰቡና ለአካባቢው ተጠያቂነት ከሌለው ዘላቂነት የለውም፡፡ ማኅበረሰቡ ገበያው ሲሆን አካባቢው ደግሞ የምርቱ ግብአት መገኛ የተፈጥሮ ስጦታ ነው፡፡ ለቢዝነስ ቀጣይነት፣ ከእነዚህ ክፍሎች ጋር ኃላፊነት የተሞላበት ግንኙነት ከሌለ ለወደፊት ችግር ይፈጥራል” ብለዋል፡፡ ዓለምአቀፍ ቢዝነስ በዚህ መንገድ የተቆራኘ ነው፡፡ በአገራችን የግሉ ዘርፍ ከዕድሜው ለጋነትና ከኢኮኖሚው ኋላቀርነት የተነሳ ብዙ የሥነ ምግባር ግድፈቶች እየታዩ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ቀለል ባሉ ነገሮች ላይ የሚታዩት የዋጋ መናር፣ የጥናት ጉድለት፣… በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ያሳያል፡፡ ኢኮኖሚው ማደግ ካለበት፣ ለማኅበረሰቡና ለአካባቢ ያለንን ኃላፊነት ከወዲሁ እየገነባን መሄድ አለብን ብለዋል፡፡ የሥነ ምግባር መመሪያውን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ሌላው ምክንያት ለደንበኞቻችንና ለአካባቢያችን ተጠያቂ የምንሆንበት መንገድ መገንባት ስላለብን ነው፡፡ ምክንያቱም ደንበኞቻችንና አካባቢያችን፣ ለቀጣይ ቢዝነሳችን መሠረቶች ስለሆኑና ንግድ ም/ቤቱ በእነዚህ ነጥቦች ላይ በሚገባ መሠራት እንዳለበት ስላመነ የተለያዩ አገራት ልምድና ተመክሮ ተመርምሮ፣ ሦስትና አራት ጊዜ በተደረጉ ወርክሾፖች ግብአት ዳብሮ፣ ሌሎች የቢዝነስ ተቋማት ከዚህ ውስጥ እየተወሰዱ ለየተቋማቸው የሚመጥን የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲያወጡ የተዘጋጀ ሞዴል መመሪያ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡
እያንዳንዱ ድርጅት፣ ፋብሪካም ሆነ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ከዚህ ከዋናው ሞዴል ጋር በማጣጣም የራሱን እንቅስቃሴ በሚመጥን መልኩ ተግባራዊ የሚያደርግበት ቀጣይ ሥራ ይኖራል፡፡ ይህን መመሪያ ተግባራዊ ያደረጉ ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ በቀጣይነት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ እንዳልካቸው፤ ይህን የሥነ ምግባር መመሪያ ተግባራዊ ያለማድረግ የሚያስከትለውን አደጋም ሲገልፁ፣ በውጭ አገራት ባደገ ኢኮኖሚ ውስጥ ተሰማርተው የሚሰሩ የውጭ ኢንቨስተሮችና ነጋዴዎች ቢዝነስ በሚሰሩባቸው አገራት የለመዱት አሰራር አለ፡፡ በእነዚያ አገሮች ህግና ስርዓት ያለው ሞራላዊ እንቅስቃሴ የተለመደ ነው፡፡ እዚህ መጥተው ለመስራት ያንን የለመዱትን የስነ ምግባር መመሪያ ይጠይቃሉ፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች ጥሬ ዕቃ ሲገዙ፣ ምርት ሲያዘዋውሩ፣ ሲሸጡ፣ ከመንግስትና ከተለያየ አቅጣጫ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ሁሉ፣ የስነ ምግባር መመሪያ የስራቸው ማቀላጠፊያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በስነ ምግባር መመሪያ የታነፁ አቅራቢ ይፈልጋሉ፡፡ የተበላሸ ጥሬ እቃ የሚያቀርቡላቸው፣ በዋጋ የሚያጭበረብሯቸው ፣ … በሂደት እየጠፉ ይሄዳሉ፡፡ እነዚህ የውጭ ኢንቨስተሮች ግብር እየከፈሉ፣ ሌሎች ግብር የማይከፍሉ የንግድ ሰዎች በገበያው ውስጥ ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት እንዳይፈጥሩ ይረዳቸዋል፡፡ እዚህ አገር ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የተመረተ ምርት ውጭ አገር ሲላክ እንደማይሸጥላቸው ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ የህፃናት የጉልበት ብዝበዛ፣ የአካባቢ ብክለት… ባለበት ሁኔታ የተዘጋጀ አበባም ሆነ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች የአመራረት ስርዓት በሌለው መንገድ ሲመረት በዓለም አቀፍ ገበያ እንደማይሸጥላቸው ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ይዘው የመጡትን ገበያ አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ የሥነ ምግባር መመሪያውን ይፈልጉታል ማለት ነው በማለት አብራርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአገራችን የቢዝነስ ሰዎች የስነ ምግባር መመሪያ ካልተከተሉ ከውጭ አገር ባለሀብቶች ጋር በሽርክና ለመስራትና ለመወዳደር አይችሉም፡፡ ያለ ስነምግባር መመሪያ መስራት ትርፉ ውድቀት፣ በመመሪያ መስራት ለራስ ብልጽግና ለአገር ዕድገት ጠቃሚ መሆኑን ብዙ የቢዝነስ ሰዎች ስለተረዱና በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ስለሚሰጣቸው መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ችግር እንደማይገጥማቸው የንግድ ም/ቤቱ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

“ያለው ጥሬ ዕቃ ከሦስት ዓመት በላይ አያስኬደንም”

በኢትዮጵያ ብቸኛው የአልሙኒየም አምራች ኩባንያ “ኢንተር አፍሪካ ኤክስትሩዥን”፤የጥሬ እቃ አቅርቦቱን በማዕድን ቁፋሮ ለማግኘት በማቀድ ለማዕድን ሚኒስቴር የፈቃድ ጥያቄ ማቅረቡን ገለጸ፡፡ ቃሊቲ ቁስቋም ማሪያም አካባቢ የሚገኘውና ከ10 ዓመት በፊት በ45 ሚሊዮን ብር የተመሰረተው ኩባንያው፤በአሁኑ ሰዓት የጥሬ እቃ ግብአቱን ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግና ከአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የሚያገኝ ቢሆንም በአገር ውስጥ ያለው አቅርቦት ከሶስት ዓመት በላይ እንደማያስኬድ የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሃይማኖት አባተ ተናግረዋል፡፡ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማምጣት የግድ ጥሬ እቃው ባለበት አካባቢ ቁፋሮ ማካሄድ አስፈላጊ በመሆኑ ፕሮፖዛሉን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆነ ሰሞኑን ኩባንያውን ለጋዜጠኞች ባስጎበኙበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት የአልሙኒየም ፕሮፋይሎችን ከውጭ በማስመጣትና በመገጣጠም ሥራ ላይ ተሰማርቶ እንደነበር የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ ከብዙ ጥናትና ሃሳብ በኋላ ግብአቶቹን  በአገር ውስጥ ለማምረት ኩባንያው መመስረቱንና በቀን 15 ቶን አልሙኒየም የማምረት አቅም ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ “ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት የተለያዩ እድገቶችን እያሳየ በማምጣቱ፣ ካፒታሉም ወደ 60 ሚሊዮን ብር አድጓል” ያሉት አቶ ሃይማኖት፤ 650 ለሚደርሱ ሰራተኞችም የሥራ እድል ፈጥሯል ብሏል፡፡  
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት የሚጠቀማቸው ጥሬ እቃዎች፡ ፓወር ኬብሎች፣ የኮካ ቆርቆሮዎችና መሰል ቁሳቁሶችን ሲሆን ፓወር ኬብሉን ሜቴክ ሲያቀርብ፣ ሌሎቹን አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡ “ይህም ሆኖ የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት አለ” የሚሉት አቶ ሃይማኖት፤ተጨማሪ ጥሬ እቃ እንደ ኬኒያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ሌሎች ጎረቤት አገሮች ለማስመጣት የአጭር ጊዜ እቅድ መያዙን፣ በረጅም ጊዜ እቅዱ ደግሞ ማዕድን ሚኒስቴር ምላሽ ሲሰጥ የማዕድን ቁፋሮውን በመጀመር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት መታሰቡን ተናግረዋል፡፡
“እኛ በወር የምናመርተው የአልሙኒየም መጠን 450 ቶን ነው፤ የአገር ውስጥ ፍላጎቱ ግን በወር 400ሺ ቶን ነው” በማለት ያስረዱት አቶ ሃይማኖት፤ ኩባንያው አሁን ባለበት አቅም የጥሬ እቃ እቅርቦትና የቦታ ጥበት ባይገድበው የአገር ውስጥ ፍላጎቱን የመሸፈን አቅም እንዳለው በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡ አልሙኒየም የማይዝግ፣ በአየር ለውጥ የማይሞቅና የማይቀዘቅዝ፣ ክብደቱም ቀላል እንደሆነና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በአገር ውስጥ አልሙኒየም የሚያመርቱ ኩባንያዎች ቢበራከቱ አገሪቱን ከውጭ ምንዛሬ ከማዳናቸውም በተጨማሪ በርካታ የስራ እድሎችንና  ፉክክርን በመፍጠር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው ከ36 ዓይነት በላይ መጠንና አይነት ያላቸው የአልሙኒየም ምርቶችን የሚያመርት ሲሆን   አንድ ኪሎ ግራም አልሙኒየም በ98 ብር ለገበያ እንደሚያቀርብ፣ ከውጭ የሚገቡት ግን በኪሎ ግራም እስከ 125 ብር እንደሚደርሱ ተጠቁሟል፡፡
ፋብሪካው ወደ ስራ በገባበት ወቅት  በርካታ ፈተናዎች እንደነበሩበት የሚያስታውሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ብዙ ሃይልና ውሃ የሚጠቀም እንደመሆኑ እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት 160 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በመቆፈር፣ የከርሰ ምድር ውሃ ማውጣቱንና ከኩባንያው አልፎ የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የሃይል መቆራረጡን ለማስቀረትም ትልልቅ ጀነሬተሮችን በማስገባት በሶስት ፈረቃ ለ24 ሰዓት ይሰራል ብለዋል፡፡ ሌላው ፈተና ከውጭ ምርት ጋር መፎካከርና የአገር ውስጥ ምርቶቻቸውን ጥራት ማሳመን እንደነበረ ያወሱት አቶ ሃይማኖት፤ አሁን እነዚያን ሁሉ ፈተና በማለፍ ገበያ ውስጥ መግባቱንና የአቅርቦት እንጂ የገበያ እጥረት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት አልሙኒየም ከማምረትም ውጭ በሰንጋ ተራ እና በቃሊቲ አካባቢ የሚገኙ 40/60 የጋራ መኖሪያቤቶችን የማጠናቀቂያ ስራ ከመንግስት ወስዶ የማጠናቀቂያ ስራዎችን እየሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡ “ኢንተር አፍሪካ ኤክስትሩዥን” ኩባንያ፤ በሥራ ጥራትና በሥራ አመራር ብቃት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ለማግኘት እንደቻለ በጉብኝቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

“ጣይቱ” የተሰኘው ዘፈን፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ስለሚቀርብ የምታውቁት ይመስለኛል። ታዋቂዋ ድምፃዊት አስቴር አወቀ በተጋባዥነት ያዜመችበት አይደለም እንዴ? በዚያ ላይ ዘፈኑ የሚጀምረው፤ ለህፃን ለአዋቂው እንግዳ ባልሆነ ነባር ዜማ ነው - “እቴ ሜቴ፣ የሎሚ ሽታ” / “ያ ሰውዬ፣ ምናለሽ ማታ” የሚለው ግጥም በሚዘፈንበት ዜማ።
በአስቴር የታጀቡት ወጣት ድምፃዊያን፣ በዚሁ የ“እቴ ሜቴ” ዜማ ነው፤ ጥያቄ ያዘለ አዲስ የአድናቆትና የውዳሴ ግጥም የሚዘፍኑልን።
ኩሩ ንግስት፣ የሴት አርበኛ
አትንኩኝ ባይ፣ ፍርድ አወቅ ዳኛ
ለነፃነት፣ ፋና የሆነች
ብልህ ጀግና፣ እመቤት ማነች?
ጥያቄውን እንድትመልሱ እየጋበዝኳችሁ አይደለም። ዘፋኞቹ መልሰውታል። ብልኋ ጀግና እቴጌ ጣይቱ እንደሆነች ነግረውናል። ይልቅስ ከግጥም መሰረታዊ ባህርያት መካከል አንዱን ወይም ሁለቱን በቀላሉ አንጥረን ለማውጣት ሊረዳን የሚችል ሌላ ጥያቄ ላንሳ።
መቼም፣ በዘፈቀደ ሁለት ግጥሞችን አምጥተን፣ በተመሳሳይ ዜማ ልናንጎራጉራቸው ብንሞክር፣ ሁልጊዜ ይሳካል ማለት እንዳልሆነ ታዝባችሁ ይሆናል። እቴጌ ጣይቱ “ኩሩ ንግስት” ተብላ የተወደሰችበት ግጥም ግን፣ በነባሩ የ“እቴ ሜቴ” ዜማ ሲቀነቀን እንከን አልተፈጠረም። ለምን? ሁለት ግጥሞች፣ በአንድ አይነት ዜማ ያለ እንከን መቅረብ የሚችሉት ምን ሲሆኑ ነው? ጥያቄውን ለመመለስ ስንሞክር፤ “ቀለም”፣ “ምት” እና “ምጣኔ” ከተሰኙት የግጥም ባህርያት ጋር በግላጭ እንገናኛለን። እዚህ ላይ፣ “ይሄ ይሄማ፣ የቋንቋ ምሁራንን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ ነው” ለማለት የሚቸኩል ሰው ካለ ተሳስቷል። በጣም በጣም ተሳስቷል።
“ቀለም”ን (syllableን) ለይቶ ለማወቅ አቅም የሌለው ሰውኮ፤ በቅጡ መናገርና ማንበብ አይችልም። “ከብት ቀልባ አደለበች” እና “ኳስ ቀልባ ወሰደች” የሚሉ ዓረፍተነገሮች ውስጥ፣ የ“ቀልባ” አነባበብ እንደሚለያይ ካወቅን፣ የ“ቀለም”ን ምንነት መረዳት እንችላለን።
ሊነጠሉ የማይገባቸውና አዋህደን የምናወጣቸው የንግግር ድምፆች ናቸው - ቀለሞች። ኳስ መያዟን ስንገልፅ፣ የ‘ቀ’ እና የ‘ል’ ድምፆችን ለያይተን አናወጣም - ተዋህደው አንድ ቀለም ይሆናሉ። [ባ’] ደግሞ ሌላ ቀለም፡፡ ስለዚህ፣ [ቀል’ባ’] እንላለን - ባለሁለት ቀለም ነው። ቀ እና ል እንዲነጣጠሉ ካደረግን ግን፣ ትርጉሙ ይቀየርና፤ ኳስ መቅለብን ሳይሆን ከብት መቀለብን የሚገልፅ ባለ ሶስት ቀለም ቃል ይሆናል - [ቀ’ል’ባ’]።
እንዳያችሁት፣ ጉዳዩ ያን ያህልም የሮኬት ሳይንስ አይደለም። ጥቂት ምሳሌዎችን ጨማምረን ብንመለከት፣ የቀለምን ምንነት አጥርተን መረዳት አያቅተንም። ለነገሩማ፤ “ቀለም”ን ለይቶ መገንዘብ፣ በቅጡ ከመናገርና ከማንበብ ጋር የተቆራኘ አይደል? ቢዘገይ ቢዘገይ፣ ከአንደኛና ከሁለተኛ ክፍል ጀምሮ የቋንቋ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት የሚደረገው ለምን ሆነና!
“ምት” እና “ምጣኔ”ም፣ ውስብስብ የካልኩለስ ቀመሮች አይደሉም። የቱን ያህል ቀላል መሰሏችሁ? ምት እና ምጣኔን ለመገንዘብ አቅም የሌለው ሰው፣ በተናጠል እና በጥንድ ነገሮችን የመቁጠር ተስፋ የለውም። በተናጠልና በጥንድ የመቁጠር አቅም ካለን ግን፤ ወይም ከከበሮ ጋር ማጨብጨብና ባለ ሁለት ስንኝ ዜማ ማንጎራጎር የምንችል ከሆነ ግን፤ ፈፅሞ አንቸገርም። ከ“ቀለም” በተጨማሪ፤ የግጥም መሰረታዊ ባህርያት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የሁለቱን (ማለትም የ“ምት” እና የ“ምጣኔ”ን) ምንነት በቀላሉ መረዳት እንችላለን። የግጥም መሰረታዊ ባህርያትን ከተረዳን ደግሞ፤ የግጥም አይነቶችን በወጉ ለይተን መገንዘብ አያቅተንም። ይህንን በምሳሌ ለማሳየት እሞክራለሁ።
አሳዛኙ ነገር ምን መሰላችሁ? የግጥም አይነቶች ላይ እንደ ማስተማሪያ የሚያገለግል ጥናትና ማብራሪያ ያቀረቡ ምሁራን፤ በመሰረታዊ ነገሮች ላይ ሳይቀር የተምታታና እርስ በርስ የሚጣረስ ሃሳብ ከየአቅጣጫው ይሰነዝራሉ፡፡ ብላታ መርስዔኀዘን ወልደቂርቆስ፣ አለማዮህ ሞገስ፣ መንግስቱ ለማ፣ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ተሾመ ይመር፣ ብርሃኑ ገበየህ…ምን ያህል በሃሳብ እንደሚለያዩ ካሁን በፊት በጥቂቱ አሳይቻለሁ፡፡ በእርግጥ መርስዔኅዘንና አለማየሁ በተወሰነ ደረጃ የግጥም አይነቶችን በመዘርዘር ፈርቀዳጅ በመሆናቸው አንዳንድ ስህተቶች ቢፈፅሙ ነውር አይደለም፡፡ መንግስቱ ለማ እና ፀጋዬ ገብረመድህንም፣ በተለይ የ “ምት” ምንነት ትኩረት እንዲያገኝ መጣራቸው ያስመሰግናቸዋል - ጥረታቸው ተዘንግቶ “ምት” የሚባለው ነገር እየተረሳ ቢመጣም፡፡ በየፊናቸው የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ቢያበረክቱም፤ ስህተት መፈፀማቸውና ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአንዱ ወደ ሌላው ስህተት እየተባባሰ መምጣቱ ግን ያሳዝናል። ሌላ ሌላው ቢቀር በ“ቀለም” ምንነት ላይ የተምታታና የሚጋጭ ሃሳብ ሲያቀርቡ አይገርምም?
ለምሳሌ፣ ሰውዬው በየቦታው ያገኘውን ጨርቅ በዘፈቀደ በላይ በላይ እየደረበ ሲለጣጥፍ እንደነበረ ለመግለፅ “ደርቶ” ብለን የምንጠቀምበት ቃል፣ ባለሦስት ቀለም ነው - [ደ’ር’ቶ’]። ገበያ መሟሟቁን ለመግለፅ “ደርቶ” የሚለውን ቃል ስንጠቀምስ፣ ከሁለት ቀለሞች የተዋቀረ መሆኑን መናገርና ለይቶ ማሳየት ምኑ ይከብዳል? [ደር’] አንድ ቀለም ነው፣ [ቶ’] አንድ ቀለም ነው። በቃ። አንዳንዶቹ ምሁራን ግን፤ ‘ር’ ቀለም ነው ወይስ አይደለም፤ ይቆጠራል ወይስ አይቆጠርም የሚባል ትርጉም የለሽ ጥያቄ እያመጡ፤ ቀለሞቹ ‘ደ’ እና ‘ቶ’ ናቸው በማለት ይደመድማሉ። ከእነዚህ ቀለማት የሚዋቀር ቃል ቢኖር ኖሮ፣ ‘ደቶ’ ይሆን ነበር።
የ‘ደርቶ’ ቀለሞች ግን፣ እንደደረተ ስንገልፅ ሶስት ናቸው [ደ’][ር’] እና[ቶ’]። እንደደራ ስንገልፅ ደግሞ፣ ቀለሞቹ [ደር’] እና [ቶ’] ናቸው። ይሄኮ ግልፅ ነው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? በአማርኛ ባንማረው እንኳ syllable ብለን በእንግሊዝኛ ተምረነው የለ እንዴ? እንዲያ አይነት ቀሽም ስህተት መፈፀማቸው ያነሰ ይመስል፤ ነገሩን እንደ ሮኬት ሳይንስ አካብደው ነው የሚያቀርቡት።
ምን ይሄ ብቻ። ብርሃኑ ገበዮህ ደግሞ፣ “ቀለም” የሚባለው ነገር፣ ጭራሽኑ ጭራና ቀንድ እንዲያጣ አደረጉት።
የአማርኛ ስነግጥም በሚል ርዕስ አቶ ብርሃኑ ባሳተሙት መፅሃፍ ውስጥ፣ ስለቀለሞች ምንነት ካሰፈሯቸው ስምንት መመሪያዎች መካከል፣ ስንቶቹ ስህተት እንደሆኑ ብታውቁ! ስምንቱም ስህተት ናቸው (ገፅ 230-32)፡፡
የ‘አ’ ቤት ሰባት ሆሄያት (ኧ፣ ኡ፣ ኢ፣ አ/ኣ፣ ኤ፣ እ፣ ኦ)፣  በቃል መነሻ፣ መሃልና መድረሻ ራሳቸውን ችለው እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ፤ “ስለዚህ ቀለም ይሆናሉ” ብለዋል። ይሄ አባባል ምን ያህል ዝርክርክር አባባል እንደሆነ ለማየት ብዙ መመራመር አያስፈልገንም። ራሳቸው አቶ ብርሃኑ በጥቂት መስመሮች ልዩነት ነው፣ ይህንን የሚያፈርስ ሌላ መመሪያ የሚያቀርቡልን። ‘እ’፣ በቃል መሃልና በመድረሻ ይቅርና በቃል መነሻ ላይ ቢገኝም ቀለም አይሆንም ይላሉ። ይህን የተሳሳተ መመሪያም ብዙ አያቆዩትም፡፡ በገፅ 239 ምሳሌዎችን ሲያቀርቡ፣ ‘እዚያ’ በሚል ቃል ውስጥ “እ” ራሱን የቻለ ቀለም እንደሆነ አስፍረዋል። ‘እንደ’፣ ‘እኩል’፣ ‘እሳት’ የሚሉ ቃላት ላይም፣ “እ” ራሱን የቻለ ቀለም እንደሆነ ገልፀዋል -  (ገፅ 245 /6 /7 በተከታታይ)። አንዱን የተሳሳተ መመሪያ በሌላ ሽረው፤ እሱንም በተቃራኒ ምሳሌ አፈረሱት።
ሌላ ሦስተኛ መመሪያ እንመልከት። የ‘አ’ ቤት ሆሄያት፣ ከፊታቸው ‘የ’፣ ‘ከ’ ወይም ‘በ’ የሚል ቅጥያ ካለ፣ ቀለም አይሆኑም ይላሉ - አቶ ብርሃኑ። ይህም ዝርክርክ አባባል ነው። ‘የአገር’ የሚለውን ቃል ‘ያገር’ ብለን እናነበዋለን ለማለት ነው የፈለጉት። ግን ከፈለግን [የ’አው’ሮ’ፓ] አልያም [ያው’ሮ’ፓ’] ብለን ማንበብና መናገር እንችል የለ? [የ’ኢት’ትዮ’ጵያ’]፣ ወይም [የ’ኢት’ዮጵ’ጵያ’] ወይስ ... በብርሃኑ መመሪያ[የ’ትዮ’ጵያ] ብንል ይሻላል?
አራተኛው መመሪያ ደግሞ፣ እያንዳንዱ ፊደል የተናባቢና የአናባቢ ቀንጅት ስለሆነ፣ ሁሉም እንደ ቀለም ይቆጠራሉ የሚል ነው። ሳድሶችም ጭምር። ለምሳሌ ‘ል’፣ የምን ቅንጅት ነው? የ‘ል’ እና የ‘እ’። ማለትም ል=ል+እ ይሆናል ይላል የብርሃኑ መመሪያ። የመጀመሪያው ‘ል’ እና የኋለኛው ‘ል’ እንዴት ይሆን የሚለያዩት? የመጀመሪያው ሳድስ ነው፤ ኋለኛውም ሳድስ ነው። እናም በአቶ ብርሃኑ ስሌት ሁለቱም የ‘ል’ እና የ‘እ’ ቅንጅት ናቸው። ስለዚህ፣ ል=ል+እ= (ል+እ)+እ= {(ል+እ)+እ} +እ ... እያለ ወደሚቀጥል ትርጉም የለሽ ቀመር ልናመራ ነው። እንዲህ የተምታታባቸው ለምን መሰላችሁ?
ቀደም ሲል “ደርቶ” የሚል ምሳሌ ሳቀርብ፤ ሁለት የተለያየ አነባበብና ትርጉም እንዳለው ጠቅሰን የለ? በእንግሊዝኛ ብንፅፈው ይሻላል መሰለኝ። እንደደራ የምንገልፅበት [ደር’ቶ’ (der’to’)] የሚለው ቃል ውስጥ፣ ‘ር’ ተናባቢ ነው። እንደደረተ የምንገልፅበት [ደ’ር’ቶ’ (de’ri’to’)] የሚለው ቃል ውስጥ ግን፣ ‘ር’ የአናባቢና የተናባቢ ጥምረት ነው፤ [ri] ብለን ለማሳየት የምንሞክረውም በዚሁ ምክንያት ነው። በአማርኛ ፅሁፍ፣ ሳድሶች ሁለት አይነት ድምፆችን ነው የሚወክሉት። አቶ ብርሃኑ፣ እየተምታታ ያስቸገራቸው፣ ይሄ ነው። ለአፍታ ያህል በማሰብ ነገሩን ማጥራት አለመቻላቸው ያስገርማል፡፡ የ‘ደርቶ’ ትርጉሞችና አነባቦች ከጭንቅላታችን በላይ መጥቀው ናላችንን ያዞሩታል እንዴ? በንባብ ወይም በንግግር ላይ በሚኖራቸው ድምፅ ነው የምንለያቸው።
ወደ አምስተኛው የተሳሳተ መመሪያ እንሸጋገር። ሁለት ሳድሶች በቃል መነሻ ላይ ሲመጡ፣ የመጀመሪያው ጠብቆ ስለሚነበብ ቀለም ይሆናል ይላል መመሪያው። አንደኛ ነገር፣ መጥበቅና መላላት ከቀለም ብዛት ጋር ግንኙነት የለውም። የሆነ ሰው መናገሩን ለመግለፅ፣ ‘አለ’ ስንል ሁለት ቀለም ነው [አ’ለ’]። መኖሩን ለመግለፅ፣ ‘አለ’ ስንልም ሁለት ቀለም ነው - [አል’ለ’]። የቀለሞቹ ብዛት ሳይሆን የቀለሞቹ አይነት ነው የሚለያየው - ይጠብቃል አይጠብቅም የምንለውም በዚሁ ምክንያት ነው። ሁለተኛ ነገር፣ ሁለት ሳድሶች በቃል መነሻ ላይ ሲመጡ አንደኛው ቀለም ይሆናል፣ ሌላኛው ቀለም አይሆንም የሚባል ነገር የለም። ለምሳሌ፣ ‘ቅርቡ’ በሚለው ቃል ውስጥ ያሉት ሁለት ቀለማት፣ [ቅር’] እና [ቡ’] ናቸው እንጂ፣ አቶ ብርሃኑ እንደሚሉት ‘ር’ በአንዳች ተአምር ተሰውሮ [ቅ’] እና [ቡ’] የሚሉ ቀለሞችን ብቻ አናገኝም። ካገኘንም የሌላ ቃል ቀለሞች ናቸው - ‘ቅቡ’ የሚል ቃል። በዚያ ላይ ለምሳሌ “ስርቻ” በሚለው ቃል፣ ሁለት ስድሶች በተከታታይ ስለመጡ አንደኛው ቀለም ይሆናል ሌላኛው አይሆንም ማለት አይደለም፡፡ ቃሉ ባለሦስት ቀለም ነው [ስ’ ር’ ቻ’]፡፡
አቶ ብርሃኑ ቀጥለው ባያቀረቡት ሌላ የተሳሳተ መመሪያ፣ በቃል መነሻ ላይ ከሳድስ ፊደል ቀጥሎ ሌላ ሳድስ ያልሆነ ፊደል ከመጣ፣ ቀለም አይሆንም ይላሉ። ግራ የሚያጋባ ነው። ‘ለመሆኑ የሚፅፉትን ነገር ያውቃሉ?’ ያሰኛል። ለነገሩ መመሪያው ስህተት መሆኑን ማስረዳት አስፈላጊ አይደለም። ግዙፍ፣ ፅዋ፣ ጭላጭ...እነዚህ በመፅሃፋቸው ውስጥ በምሳሌነት የጠቀሷቸው ቃላት ላይ፣ ‘ግ’፣ ‘ፅ’፣ ‘ጭ’ ራሳቸውን የቻሉ ቀለሞች እንደሆኑ ራሳቸው አቶ ብርሃኑ በመግለፅ መመሪያውን ቀብረውታል - ገፅ 244።
ሰባተኛውን መመሪያ ተመልከቱ። ሳድስ፣ ጠብቆ የሚነበብ ከሆነ ቀለም ይሆናል፣ ካልጠበቀ ደግሞ ቀለም አይሆንም ይላል መመሪያው። ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት፣ መጥበቅና አለመጥበቅ ምን ማለት እንደሆነ ለይተው ስላላወቁ እንጂ፣ ከቀለም ብዛት ጋር ግንኙነት እንደሌለው በተረዱ ነበር። የመጨረሻው መመሪያ ደግሞ፣ ሳድስ የስንኝ መጨረሻ ላይ ሲሆን፣ ቀለም ይሆናል ይላል።  ከገፅ 239 እስከ 249 ድረስ በመመሪያው መሰረት የቀረቡ ምሳሌዎችን ብትመለከቱ፣ በእያንዳንዱ ገፅ ላይ ይህንኑን መመሪያ ከሚደግፉ ይልቅ የሚያፈርሱ ምሳሌዎች ናቸው የሚበዙት።
ከዚህ ሁሉ መረዳት የቻልኩት፣ አቶ ብርሃኑ ስለሚፅፉት ነገር ጠንቅቀው የማሰብ ልምድ እንዳልነበራቸውና ‘ቀለም’ (syllable) የሚባለውን ነገር በቅጡ ለመገንዘብ እንዳልሞከሩ ነው።
የቀለም ምንነትን መገንዘብ፣ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ የሚካተት ሆኖ ሳለ፣ እንዴት እንዲህ አይነት ችግር ይፈጠራል? Anne እና Klaus Wedekind፣ “Amharic stress (beat) rules of linguists, poets and singers” በሚል ርዕስ፤ በ11ኛው የኢትዮጵያ ጥናቶች አለማቀፍ ጉባኤ ላይ ጥናታቸውን ሲያቀርቡ የሰጡትን አስተያየት መጥቀስ ይቻላል። የቀለም ምንነት እንደ ውስብስብ ጉዳይ ተደርጐ መታሰቡ ግራ ያጋባቸው እነዚሁ ምሁራን፤  መንግስቱ ለማ ስለ ግጥም አይነቶች የጥናት ፅሁፍ ሲያቀርቡ፣ ግማሽ ያህሉን ቦታ ያዋሉት ስለ ቀለም ምንነት በማብራራት እንደሆነ በመጥቀስ ነው አግራሞታቸውን የሚገልፁት። መንግስቱ ለማ በቀለም ቆጠራ ላይ ባይሳሳቱም፣ የዚያን ያህል ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕስ አድርገው ማቅረባቸው ነው አስገራሚ የሆነባቸው። ብርሃኑ ገበዮህ ጭራሽኑ ቅጣምባር እንዳጠፉት አላዩማ። “ምት” እና “ምጣኔ” የሚባሉት ነገሮች ምን ያህል ድብልቅልቃቸው እንደወጣ ቢያዩስ ምንኛ ይገርማቸው ይሆን?
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት “ምት” እና “ምጣኔ”ም ውስብስብ አይደሉም፡፡ ማንጐራጐር የሚችል ሰው ሁሉ፣ በቀላሉ ሊገነዘባቸው ይችላል፡፡
ለምሳሌ፣ “ጣይቱ” የሚለው ግጥም በ “እቴ ሜቴ” ዜማ ያለ እንከን ሊቀርብ የቻለው፤ ተመሳሳይ ምት እና ምጣኔ ስላለው ነው፡፡   
ሮኬት ሳይንስ ወይም ውስብስብ የካልኩለስ ቀመር አመጣብን ብላችሁ አትስጉ። በእርግጥ፣ አንዳንድ ምሁራን ስለ “ቀለም”፣ “ምት” እና “ምጣኔ” ሲያወሩ ወይም ሲፅፉ፣ ጭላንጭሉ የማይታይ ከባድ ሚስጥር ሊያስመስሉት አይሞክሩም ማለቴ አይደለም። ይሞክራሉ። ግን ይሄ የናንተ ሳይሆን የነሱ ችግር ነው። ለሌላ ሰው እውቀት ሊያካፍሉ ቀርቶ፣ ከመነሻው ለራሳቸውም ነገሩን  ለመገንዘብ ሳይሞክሩ ወይም ሳይፈልጉ ስለቀሩ ነው። አንዳንድ ሰው፣ ፍንትው ጥርት ብሎ ከሚታይ ነገር ይልቅ፣ በብዥታ ጭጋግ ውስጥ የተድበሰበሰ ነገር ይመቸዋል። ታዲያ፣ ነገሩ ሁሉ እዚያው እንደተድበሰበሰ ቢቀር ቢመኙ ምን ይገርማል? አለዚያማ፣ የ“ምት” እና የ“ምጣኔ”ን ምንነት ለመገንዘብ ትንሽ ቢጥሩ፣ ፈፅሞ ከባድ አቀበት ባልሆነባቸው ነበር። በቅጡ ማንበብና እንደነገሩ አንድ ሁለት ብሎ መቁጠር የሚችል ሰው፤ የ“ምት” እና የ“ምጣኔ”ን ምንነት በቀላሉ መገንዘብ ይችላል - በቅጡ ጥርት ብሎ ከቀረበለት። መራቀቅ አያስፈልገውም። እንዴት በሉ።
አንዳች ዜማ አስታውሰን ማንጎራጎር እንችል የለ? ሃሃ-ሃሃ... እያልን፤ ወይም እእ-እእ... ወይም ላላ-ላላ... ወይም ነነ-ነነ... እያልን። ማንጎራጎር ከቻልን፤ ቢያንስ ቢያንስ የግጥሙን ምትና ምጣኔ በስሜት ደረጃ ይዘነዋል ማለት ነው። በተግባር ሞክሩት።
[እ’ቴ’ - ሜ’ቴ’ -- የ’ሎ’ሚ’ - ሽ’ታ’]
ቃላትን ሳትጠቀሙ፣ በእንጉርጉሮ ልታስኬዱትም ትችላላችሁ።
[አ’አ’- አ’አ’-- አ’አ’አ’- አ’አ’]
የመጀመሪያውን ስንኝ ስናንጎራጉር፣ በተከታታይ የምንፈጥራቸውን ድምፆች አስተውሉ። እነዚህ አንድ ሁለት ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉ ድምፆች፣ በስንኙ ውስጥ የሚገኙ “ቀለሞችን” በሙሉ ይወክላሉ። ቀለሞቹ በሁለት ወይም በሦስት የተጣመሩ የተቧደኑ መሆናቸውንም ልብ በሉ። [2 - 2 - 3 - 2] ሆነው ተጣምረዋል። ቀለሞቹን ያጣመርንበት ስርዓት፣ በእግር ኳስ ቋንቋ፣ “የቀለሞች አሰላለፍ” ልንለው እንችላለን። ሁለቱን ወይም ሶስቱን ቀለሞች እያጣመርን የምናንጎራጉረው በምን ምክንያት ይሆን? የቀለሞቹን አሰላለፍ የምንፈጥረው፣ አንዱን ቃል ከሌላኛው ቃል በመለየት ሊመስል ይችላል። ግን አይደለም። ሁለተኛውን ስንኝ በማንጎራጎር አረጋግጡ።
[ያ’ሰ’ - ው’ዬ’ -- ም’ና’ለሽ’ - ማ’ታ’]
ድምፆቹን የምናጣምራቸው ቃልን ከቃል በመለየት ቢሆን ኖሮ፣ [ያ’ - ሰ’ው’ዬ’] የሚል እየሆነብን ዜማው ይዛባብን ነበር። ዜማው ትክክል የሚመጣልን፣ የድምፆቹን ጥምረት ወይም አሰላለፍ እንደ መጀመሪያው ስንኝ [2 - 2 - 3 -2] ስለምናደርገው ነው። የሁለቱም ስንኞች የቀለም አሰላለፍ ይገጥማል።
የጣይቱ መነሻ ግጥም የቀለም አሰላለፍም ተመሳሳይ ነው [2-2-3-2]፡፡ ቀለሞቹ በጥንድ ወይም በስሉስ የተጣመሩበት ቅደም ተከተል “ምት” ይባላል፡፡ በየስንኙ ምን ያህል ጥንዶች ወይም ስሉሶች እንዳሉ ስንገልፅ ደግሞ “ምጣኔ”ውን እየተናገርን ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ

የዳንስ ውድድር፣ ኮሜዲ፣ የፍቅር ዜማዎች፣ እራትና ወይን ጠጅ
የሆቴሎቹ የመዝናኛ ክፍያ ከ600 ብር - 5ሺ ብር ይደርሳል

   በዛሬው ዕለት በመላው ዓለም የሚከበረውን የፍቅረኞች ቀን (Valentine’s day) ምክንያት በማድረግ አዲስ አበባን ጨምሮ በሃዋሳ ቢሾፍቱና ላንጋኖ የሚገኙ ትልልቅ ሆቴሎች ለፍቅረኞች ምሽት ሽርጉድ እያሉ ሲሆን ለለያዩ መዝናኛዎች ከ600 ብር እስከ 5ሺ ብር ይጠይቃሉ፡፡ የቀይ አልባሳት ገበያ መድራቱንም ነጋዴዎች ገልፀዋል፡፡
አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ጐዳና ላይ የሚገኘው ንግስተ ሳባ ሆቴል ዛሬ ማታ ልዩ የፍቅረኞች ምሽት ያዘጋጀ ሲሆን የተለያዩ የፍቅር ዜማዎችና ግጥሞች ይቀርቡበታል ተብሏል፡፡ አርቲስት አስቴር በዳኔ የንግስተ ሳባን የፍቅር ታሪክ በአጭር ድራማና መነባንብ መልክ ለታዳሚዎች ታቀርባለች፡፡ ንግስተ ሳባ ሆቴል ከአብርሃም ግዛው ኢንተርቴይንመንትና የፕሬስ ስራዎች ድርጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ ልዩ የፍቅር ምሽት፤ በጥንዶች መካከል የሳልሳ፣ የትዊስትና ዋልዝ ዳንሶች ውድድር የሚካሄድ ሲሆን ለሶስት አሸናፊ ጥንዶች ለእያንዳንዳቸው አምስት ሺ ብር የሚያወጣ የእራት፣ የአልጋና የቁርስ ግብዣ ይደረግላቸዋል፤ ብሏል - ጋዜጠኛና ፕሮሞተር አብርሃም ግዛው በምሽቱ ዝግጅት የኮሜዲ ስራዎች የሚቀርቡ ሲሆን ፕሮግራሙን ታዋቂ አርቲስቶች ይታደሙታል ተብሏል፡፡
በማማስኪችን እንዲሁ የፍቅረኞች ምሽት የተዘጋጀ ሲሆን አንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ በስራዎቹ ታዳሚውን ያዝናናል ተብሏል፡፡ መግቢያ 50 ብር እንደሆነም ታውቋል፡፡ በቫራይቲ ሬስቶራንት የፍቅረኞች ምሽት ዛሬ 11፡30 የሚጀምር ሲሆን ልዩ የእራት ፕሮግራም፣ የዲጄ ሙዚቃ፣ ለጥንዶች የሚበረከት ሰርፕራይዝ ስጦታና ሌሎች ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል፡፡
ኔክሰስ ሆቴል፤ ልዩ የቡፌ እራት ከልዩ ልዩ የወይን ጠጆች ጋር ያሰናዳ ሲሆን የቫዮሊንና የፒያኖ ሙዚቃ ይቀርባል፡፡ ሰርፕራይዝ ስጦታም ይኖራል ተብሏል፡፡ የብራይት ካፌ የፍቅረኞች ምሽት ፕሮግራም የሚጀምረው ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ሲሆን ከ10 በላይ ድምፃዊያን በአኩስቲክ ባንድ ታጅበው ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሳልሳ ዳንስ፣ ስታንዳፕ ኮሜዲና ሌሎች አዝናኝ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ታውቋል፡፡ ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስና እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ቴዎድሮስ መኮንን (ቴዲ ማክ) በክብር እንግድነት እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡ በሳሮ ማሪያ ሆቴል ደግሞ ለፍቅረኞች ልዩ የእራት ፕሮግራም፣ ሰርፕራይዝ ስጦታዎችና ሌሎች ዝግጅቶች እንዳሉ ታውቋል፡፡
ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ የሚገኘውና ባለፈው አመት የተከፈተው ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል፤  ልዩ የፍቅረኞች ምሽት ያዘጋጀ ሲሆን የጥንዶች መግቢያ 600 ብር ነው፡፡  ሆቴል ሲዮናትም ልዩ የፍቅረኞች ምሽት ማዘጋጀቱን ጠቁሟል፡፡ ልዩ ልዩ የፍቅር ሙዚቃዎች በዲጄ የሚቀርቡ ሲሆን፤ የጥንዶች መግቢያ 900 ብር ነው ተብሏል፡፡ ከነአንካሬ ዛሬ ምሽት ከ12 ሰዓት ጀምሮ ነው በሩን ለፍቅረኞች ክፍት የሚያደርገው፡፡ ልዩ የብፌ እራት እንዲሁም የዲጄ ሙዚቃም አሰናድቷል፡፡
ሃዋሳ የሚገኘው ኬራውድ ሆቴል፤ ፕሮግራሙን ከዋዜማው ምሽት የጀመረ ሲሆን የዲጄ ሙዚቃ፣ ልዩ የወይን ጠጅ እንዲሁም ልዩ እራት በማሰናዳት ፍቅረኞች ዕለቱን መቼም  እንዳይዘነጉት ለማድረግ እየታተረ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የአዲስ አበባው ዩጐቪያ ክለብ በበኩሉ የምሽቱን ታዳሚዎች የሚያዝናናው ከተወዳጁ ድምፃዊ አብነት አጐናፍር ጋር እንደሆነ ገልጿል፡፡ ጥንዶች ይሄ የደመቀ የፍቅረኞች ምሽት እንዳያመልጣቸው የግብዣ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የቢሾፍቱው ፒራሚድ ሪዞርት፤ የጥንዶች ውድድርና የፍቅር ፊልሞችን ለታዳሚዎቹ ያዘጋጀ ሲሆን ልዩ እራት ከልዩ የወይን ጠጅ ጋር ማሰናዳቱንም ጠቁሟል፡፡ ሀርመኒ ሆቴልም እንዲሁ ሚካኤል ለማን ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር አቀናጅቶ ምሽቱን ለፍቅረኞች ውብና አስደሳች ለማድረግ መዘጋጀቱን ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ልዩ እራት ከወይን ጋር፣ የኮሜዲ ምሽትና የፍቅረኞች ስጦታ አዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡ በሃርመኒ ሆቴል ምሽቱን ለማሳለፍ ላቀዱ ጥንዶች 1800 ብር፣ ብቻውን ለመጣ 900 ብር ይከፍላሉ፡፡
በደብረዘይት የሚገኘው አሻም አፍሪካ ሪዞርት፤ ለምሽቱ ልዩ ራት ከዋይን ጋርና የዲጄ ሙዚቃ ያዘጋጀ ሲሆን በሪዞርቱ የፍቅረኞች ምሽትን ለመታደም የሚሹ ጥንዶች 219 ዶላር ወይም 4423 ብር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቦሌ የሚገኘው ፍሬንድሺፕ ሆቴልም የፍቅረኞችን ቀን አይረሴ ለማድረግ ዛሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሩን ለእንግዶቹ ክፍት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ የተለያዩ የፍቅር ዜማዎች፣ ሰርፕራይዝ ስጦታዎችና ሌሎች…ፕሮግራሞችም እንደሚኖሩ ገልጿል፡፡
ሳሚ ካፌና ሬስቶራንትም እንዲሁ ልዩ የፍቅረኞች ምሽት ማዘጋጀቱን ገልጿል፡፡ አኩስቲክ ባንድ ምሽቱን እንደሚያደምቀውና ዳዊት ፍሬውም ክላርኔት እንደሚጫወት ተጠቁሟል፡፡
ውሃ ልማት አካባቢ የሚገኘው ባለ አምስት ኮከቡ ካፒታል ሆቴል፤  ምሽቱን ለየት ለማድረግ የቀይ ምንጣፍ ልዩ የፍቅረኞች ምሽት ያዘጋጀ ሲሆን የሰባት ጥንዶች የዋልዝ ዳንስ ውድድርና ሙዚቃ አሰናድቷል፡፡ የፍቅረኞች ምሽቱን በሆቴሉ ለመታደም የሚሹ ጥንዶች 1800 ብር፣ ለብቸኛ ታዳሚ ደግሞ 1200 ብር እንደሚያስከፍል የገለፀው ሆቴሉ፤ እዚያው ተዝንተው፣ አድረውና ቁርስ አድርገው መውጣት ለሚፈልጉ 4500 ብር ይበቃቸዋል ተብሏል፡፡
ላንጋኖ ሪዞርት የፍቅረኞች ቀን ልዩ ዝግጅቱን የጀመረው ከትላንት በስቲያ ሲሆን ዛሬ  የአዝማሪ ሙዚቃ፣ የጀልባ ሽርሽር እንዲሁም ልዩ ልዩ ምግብና ወይኖችን መዘጋጀታቸውንና ጥንዶች 3600 ብር፣ ብቸኛ 1900 ብር እንደሚከፍል ተጠቁሟል፡፡ አፍሮ ዳይት ሆቴልም ልዩ የፍቅረኞች ምሽት እንዳዘጋጀ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፍቅረኞች ቀንን አምነውበት ለሚያከብሩት ብዙ አማራጮች የተዘጋጁ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ቫለንታይን የውጭ ባህል ነው በሚል የሚቃወሙትም አሉ፡፡
በ20ዎቹ መጨረሻ ዕድሜው ላይ የሚገኘው እስክንድር፤ የፍቅረኞች ቀን በአገራችን መከበሩን ከእነአካቴው አይቀበለውም፡፡ “ፍቅር በአደባባይ ልታይ ልታይ የሚባልበት ሳይሆን የልብ ትስስር ጉዳይ ነው” ያለው ወጣቱ፤ ቫለንታይን የአገራችን ባህል ስላልሆነ አልቀበለውም ባይ ነው፡፡ ቀይ መልበስና ሌሎቹም ነገሮች የእኛ አለመሆናቸውን ይናገራል፡፡ እንዲያም ሆኖ ፍቅረኛው ደሞ በቫለንታይንስ ዴይ ቀያይ ልብሶች ገዝቶ በስጦታ እንዲያበረክትላት ትፈልግ ነበር፡፡ ነገሩን ፈጽሞ ባላምንበትም ፍቅረኛዬን በጣም ስለምወዳት የማልፈልገውን አደረግሁ ብሏል፡፡  “ፍቅረኛዬ እንዳይከፋት ብዬ ቢያንስ ከውስጥ የሚውል ቀይ ፓንትና ጡት ማስያዣ ገዝቼ በስጦታ አበርክቼላታለሁ፡፡ ዋጋው ግን በጣም ውድ ነው” ሲል በመገረም ገልጿል፡፡
የ31 ዓመቱ አሳየኸኝ፤ ፍቅረኛው ለቫለንታይን እንዲገዛላት የጠየቀችው ስጦታ ዋጋው ናላውን እንዳዞረው ይናገራል፡፡ ባለፈው ዓመትም በከፍተኛ ዋጋ ምክንያት ከፍቅረኛዬ ጋር ተጋጭተን፣ ለሰባት ቀናት ተዘጋግተን ነበር ያለው አሳየኸኝ፤ “ዘንድሮም መጋጨታችን አይቀሬ ነው” ሲል የፍቅረኞች ቀን ስጋት እንደሆነበት ገልጿል፡፡
እየሰራሁ ገቢ ባገኝም እየከፈልኩ እማራለሁ፣ ወንድሜንም አስተምራለሁ የሚለው ወጣቱ፤ እንዲህ ያሉ ወጪች በእጅጉ ይጎዱኛል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል በአሜሪካ የዘንድሮው ቫለንታይን ቀን ለስጦታ የሚወጣው አጠቃላይ 18.9 ቢ.ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅና ይሄም በከፍተኛነት ወጪ ሪከርድ እንደሚሰብር ተገምቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 4.8 ቢ. ዶላር ያህሉ ለጌጣጌጥ ስጦታዎች እንደሚወጣ ሰሞኑን ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በቫለንታይን ቀን ከረሜላዎች፣ ፖስት ካርዶችና  አበቦች በስጦታነት ይበረከታሉ - የአልማዝ ቀለበትና ሌሎች ጌጣጌጦች ሳይረሱ ማለት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ አንድ የስራ ኃላፊ ስለ ቫለንታይን ቀን አስተያየታቸውን ሲናገሩ፤ “ጉዳዩ ከፍቅር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ቀኑ ቢከበር አይከፋኝም፤ አንዳንድ ነጋዴዎች ግን አጋጣሚውን በመጠቀም ትርፍ ለማግበስበስ የሚያደርጉት ሩጫ አያስደስተኝም” ብለዋል፡፡ ሴቶችም ቢሆኑ በዚህ ቀን ፍቅረኞቻቸውን ለአላስፈላጊ ወጭ በመዳረግ ማማረር የለባቸውም ሲሉ ይመክራሉ፡፡ “ውድ ስጦታ እንዲሰጣቸው ማስገደድ ፍቅርን ከማጠንከር ይልቅ ስለሚያሻክረው ጥንቃቄ ያሻል” ብለዋል፡፡ ሁሉም አምኖበት የሚያደርገው ከሆነ፣ አበባ፣ ቀይ ልብሶች የሚሸጡና የሆቴል አገልግሎት የሚሰጡ አጋጣሚውን በጤናማ መንገድ ገቢ ቢያገኙበት ክፋት እንደሌለው ጠቁመው፤ በዓሉ ወግና ስርዓት በጠበቀ መልኩ ቢከበር መልካም እንደሆነ አክለው ገልፀዋል፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 14 February 2015 14:48

የቫለንታይን ስጦታ)

የሻማ ብርሃን፣ የጨረቃ ብርሃን፣ የክዋክብት ብርሃን
      ከሁሉ ይበልጥ የሚፈካው ግን  የፍቅር
     ብርሃን፡፡
                ግሪይ ሊቪንግስቶን
ያንሾካሾክልኝ በጆሮዬ ሳይሆን በልቤ በኩል ነው፤ የሳምከውም ከንፈሬን ሳይሆን ነፍሴን ነው፡፡
ጁዲ ጋርላን
ልብ ምን ያህል እንደሚይዝ ማንም ለክቶት አያውቅም፤ ገጣሚዎችም ጭምር፡፡
ዜልዳ ፊትዝጌራልድ
ስለ አንተ ባሰብኩ ቁጥር ዘለላ አበባ ባገኝ፣ ዕድሜ ልኬን በመናፈሻዬ ውስጥ እጓዝ ነበር።
ክላውዲያ ጋንዲ
የማፈቅርሽ ውብ በመሆንሽ ነው ወይስ ውብ የሆነሽው ስለማፈቅርሽ ነው?
ኦስካር ሐመርስቴይን ሁለተኛ
ነፍሴ መድረስ በሚችልበት ጥልቀት፣ ስፋትና ቁመት  አፈቅርሃለሁ፡፡
ኤሊዛቤት ባሬት ብራውኒንግ
ከልቤ የምሻው ፍቅርን ብቻ ነው፤ አልፎ አልፎ ጥቂት ቸኮሌት ግን አይጎዳም፡፡
ሉሲ ቫን ፔልት
ህይወት አጭር ቢሆንም  ፍቅር  ረዥም ነው፡፡
አልፍሬድ ሎርድ ቴኒሰን
ቫለንታይንን የሚያህል ታላቅ ቅዱስ እንደሌለ አረጋግጣለሁ፡፡
ኦግዴን ናሽ
የመፈቀር ጸጋ አግኝቶ ማን የደኸየ አለ?
ኦስካር ዋይልድ
ነፍስና ነፍስ የሚገናኙት በፍቅረኞች ከናፍር ላይ ነው፡፡
ፔርሲ ባይሼ ሼሊ
ፍቅር በዳበሰው ጊዜ ሁሉም ገጣሚ ይሆናል።
ፕሌቶ

Published in የግጥም ጥግ

   ባለፈው ሳምንት ባቀረብኩት ጽሑፍ፤ የፊደላችን እያንዳንዱ ሆህያት በጽንፈ - ዓለም ውስጥ ያላቸውን ሠፊ ውክልናና በተሰጧቸው የቁጥር ኮድ አማካኝነት በዚሁ ጽንፈ - ዓለም የተከናወኑ፣ እየተከናወኑ ያሉትንና ወደፊትም የሚከናወኑትን ኩነቶች የማወቂያ ስልቶች እንደሆኑ በዋናነት ለማመላከት ሞክሬአለሁ፡፡
ከዚህ አንፃር የግዕዝ ፊደላት ከማንነት ቅርስነታቸው ባሻገር የምስጢር ባሕር በመሆናቸው በወጉ ሳንመረምርና ሳናውቅ ፊደላቱ ይቀነሱ፣ ይሻሻሉ ወይም ይለወጡ ማለት ሀገርን፣ ትውልድና ታሪክን ሊጠቅም እንደማይችል ማሰብ ተገቢ እንደሆነ በድጋሚ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ የፊደላችንን ጥንታዊነትና እንዲያውም ለሌሎች ቋንቋዎች ፊደላት መነሻ እንደሆነ ለማመን የሚያስችሉ የምርምር አቅጣጫዎችን መከተል እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ የግዕዝ ፊደል ተጠቃሚ ሆነን አማርኛ ቋንቋ ለመምረጥ የቻልንባቸውንም ምስጢራት አበክሮ ለማወቅ መጣጣር የጥንታዊ ማንነታችንን ለማረጋገጥ ጠቃሚ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ የራሷን ፊደል ተጠቃሚ አገር ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነች ተደጋግሞ የሚነሳ ሌላው ነጥብ ነው፡፡ በእርግጥ በፊደልና ቋንቋ ማለትም በሰው ዘር ሥነ - ልሳን አጀማመር አኳያ ታሪኩ በማያዳላ ሁኔታ ከተጠናና ወደ ነባር ቦታው ከተመለሰ አፍሪካን  የሚቀድም እንደሌለ ሊሠመርበት የሚገባ እውነት ነው፡፡ በዚህም ሐቅ መሠረት ቢያንስ በሰሜን አፍሪካ የዛሬውን ግብፅ፣ ኑቢያ፣ ሞሪታኒያና የመሳሰሉት አካባቢ በተሠማሩትና ለረጅም ዘመናት በቆዩት የካም ዘሮች የተፈጠረው ዐረብኛ ፊደል አፍሪካዊነት ብዙም የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ በዚህ እሳቤ ከሄድን የግዕዝን ፊደል በአፍሪካ “ብቸኛ” ለማለት የሚሻክር ይመስለኛል፡፡ ከዚያም በላይ በሀገራችን ሰሜኑ ክፍል ጥንታዊ የነበረው “የሳባውያኑ ፊደል” ከምን ተነስቶ የት በመድረስ እንደተተካ ወይም እንደጠፋ ባለመታወቁ እንጂ አፍሪካ የሌላም ፊደል ባለቤት እንደሆነች መናገር የሚከብድ አልነበረም።
ስለሆነም የግዕዝ ፊደልን በአፍሪካ ብቸኛ እንደሆነ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ይሰማኛል፡፡ በዚህ ረገድ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ የአፍሪካን በተለይም የካም - ኩሽ ሥነ - ልሳናትን በሠፊው ማጥናቱ የሚታወቅ ሲሆን በርካታ የጥናት ጥራዞቹ ወዴት እንዳሉ አፈላልጐ ለህትመት እንዲበቁ ወይም ለሌሎች ምርምር አመቺ በሆነ መንገድ እንዲገኙ የጉዳዩ ባለድርሻዎች በፍጥነት ሊተጉ ይገባል፡፡
በፊደላችን ጉዳይ አስተያየት ያቀረቡ ብዙ ጸሐፍት፤ በተለይ በአሁኑ ጊዜ እጅግ ያሳሰባቸው የፊደላቱ በተናጠልም፣ የሆህያቱ የአጻጻፍ ስህተቶች ያለቅጥ እየተበራከቱ የመምጣታቸው  ሁኔታ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ አቅልሎ የማየቱ አካሄድ በበኩሌ እጅግ አሳዛኝና ይቅርታ የሌለው ጥፋት መሆኑን በአንክሮ ማስረገጥ እፈልጋለሁ፡፡ ጉዳዩ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ፣ ባለዕዳ አይቀበለውም” እንዲሉ፣ በፊደላቱ ሳይሆን በራስ ማንነት ላይ በደል መፈፀም ማለት ነው፡፡ “በኪነጽሕፈት ጊዜ የፊደላት አቀማመጥ ወይም ኪነጥበብ ሥነ ጥበብ ዘጠነኛ” በሚል መጽሐፍ (ገጽ መ) “…በከተማው ስዘዋወር በዋና ዋና መንገዶችና ሱቆች የተዘረጉ ጋዜጣ፣ መጽሔትና መጽሐፍ በያሉበት የሀገራዊ ፊደል የአጻጻፍ ስልታቸውን ስመለከት ፊደላቱ ድምጻቸው በማይገለጽበት ያለ ቦታቸው እየተደነቀሩ፣ በደማቅ ቀለማትና ፎቶግራፍ ብቻ ደምቀው የሚንፀባረቁ ናቸው፡፡ ማንም ላያውቅልኝ እንደዚህ በመሳሰሉ ሁሉ ስከፋና ሳዝን ውዬ እመለሳለሁ፡፡” ሲሉ ይትባረክ ገሠሠ  ምሬታቸውን በጽኑ ይገልጻሉ፡፡ እኚህ ተቆርቋሪ በአዲስ አበባ ከተማ ሲዘዋወሩ ያዩአቸውን ተነባቢ ጽሑፎች እያመላከቱን ነው፡፡ በፖስተር፣ በድርጅትና የንግድ ስሞች፣ በባነርና በየአደባባዮቹ ታላላቅ መልዕክት እንዲያስተላልፉ የተተከሉና የቆሙ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ሁሉ የሚጽፏቸው ቃላት ፊደሎቻቸው መልዕክቱን በትክክል የማያስተላልፉ እየሆኑና አንዳንዶቹም አሰዳቢዎች መሆናቸው በርክቷል፡፡
ዛሬ በምንቸገረኝነት ወይም የማይረባ ከንቱ አስተሳሰብ ለማራመድ ተብሎ በቸልታ የሚሠራና የሚተላለፍ ጉዳይ ውሎ አድሮ ወይም በረጅም ዘመን ሂደት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ መጪው ትውልድ የሥራችንን ብላሽነት በተረዳበት ቅጽበትም ታሪካችንን ይፍቀዋል፡፡ በመሆኑም ፊደሎቹ በትክክል ስለመጻፋቸው ማረጋገጥ የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት ነው፡፡
የፊደል ሐብት ከታደሉ ጥቂት ሀገራት ውስጥ ለዚህ ታላቅ ቅርስ ሐውልት ወይም መታሰቢያ ያላቆመች ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡ ይህም ቢሆን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በየአቅጣጫው የሚነሱና ታሪክና ትውልድ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ጉድለቶች በሚመለከታቸው አካላት የማይታረሙ ከሆነና የጠቋሚዎቹ ፋይዳ “እንደ ቁራ ጩኸት” እየታየ ከታለፈ፣ ጤነኛ የዕድገት ሂደት ለመከተል እንደማይመች ከወዲሁ መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ የአገራችንን የቋንቋ ፖሊሲ ይፋ ለማድረግ እንደተዘጋጀ ተሰምቷል፡፡ የፊደሉ ቅርስነትና ሀብትነት ከህገመንግስታዊ ክብርና ጥበቃው ጋር በፖሊሲው ውስጥ እንደሚካተት ተስፋ አለኝ፡፡ የኪነ ጥበብ ዘርፉ በተለይም በድርሰት ዙሪያ የተደራጁ ማህበራት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አማካኝነት በሚሰጡት ሀሳብ መሰረት ፊደላችን ቋሚ መታሰቢያ ሊቆምለት እንደሚገባ በአጽንኦት መግለጽ ይገባኛል፡፡ ጉዳዩን ሰፋ አድርገን ካየን በአሁኑ ጊዜ ፊደላችንም ሆነ የግዕዝ ቋንቋ የህዝብ ባለቤትነት ደረጃ አግኝተው የመጠናት፣ የማደግና የመስፋፋት ዕድላቸው በከፍተኛ ደረጃ ሊታሰብበት የሚገባ አቢይ ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም የዕውቀትና የጥበብ፣ የታሪክና የማንነት አውድን በመከተል፣ በራሳችንም ኮርተን የቻልነውን ሁሉ ብናደርግ ፍሬውን ሳይዘገይ ልናይና በሥራችንም ታላቅነት ልንኮራ እንችላለን፡፡
የራስን ጉዳይ በማጉላት፣ የጎደለውንም በምርምር በማሟላት በትጋት መሥራት ያለበት በሁሉም የባህልና የታሪክ ዘርፎች ሲሆን በተለይም የትምህርት ጎራው ይህንኑ አቢይ ጉዳይ ያማከለ ቢሆን ሁኔታዎች የሚስተካከሉበት ሂደት የሚፋጠን ይመስለኛል፡፡ ክቡር ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁ /ደራሲ/ በዚህ ረገድ እጅግ ታግለው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ የትምህርቱን ዘርፍ ከታችኛው እርከን እስከ ከፍተኛው ድረስ ሀገራዊ በሆነው ማህበራዊና ባህላዊ መደላደል ላይ መመስረት እንዳለበት በጽሑፍም ሆነ በቃላቸው ሲታገሉ እንዳለፉ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡ በቋንቋ በኩልም የሚሰጠው ትምህርት፣ የግዕዝ ስነ ጽሑፍን ጭምር እንዲያካትት ሐዲስ አለማየሁና ሌሎችም ሳይታክቱ አሳስበዋል፡፡ አሁንም ተስፋ የሚጣለው በተለይ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እየተደረገ ባለው የኃላፊነት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲም የግዕዝ ቋንቋና ሥነ--ጽሑፍ ጉዳይ እየታሰበበት እንደሆነ ፍንጮች ታይተዋል፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁን የባህል ማዕከልን በመመስረት በየዓመቱ በፊደልና በቋንቋዎቻችን ዙሪያ ግዕዝንም ጭምር በርካታ የምርምር ወረቀቶች (ጥናቶች) እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ይህ ጥረትና ትጋት እየተጠናከረ ከሄደ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሂደት የጥንታዊ ቋንቋዎቻችን ጥናት ማዕከል ወይም አካዳሚ ለመመሥረት እንደሚችል ብሩህ ተስፋ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ከቆረሰው አጉርሶ፣ ከለበሰው አልብሶና የአብነት ት/ቤቶችን፣ ገዳማትና አድባራትን በመንከባከብ፣ የግዕዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ከነሙሉ ክብሩ እስከዛሬ እንዲዘልቅ ጥረቱን ሲያስተባብር ለቆየው ለጎጃም ህዝብ ትልቅ እውቅናና ልግስና ነው፡፡ ይገባዋልም፡፡ በዚያን ጊዜ የግዕዝ ሁለንተናዊ ታሪክና ሀብትነት በሚገባ ታውቆ በማያወላውል ሁኔታ ህዝብ የባለቤትነቱን ኃላፊነት ይረከባል፡፡ መንግስትም የበኩሉን ድርሻ ይወጣል የሚል እምነት ማሳደር ይቻላል፡፡
እዚህ ላይ አስረስ የኔሰውን ጠቅሼ ጽሑፌን ላብቃ፡፡ “የካም መታሰቢያ” የተሰኘውን የምርምር መጽሐፋቸውን ያቀረቡበትን ምክንያት ሲገልፁ፤ “… በእውነተኛ መንገድ እርግጠኛውን ታሪክ ለሚፈልጉ ነው እንጂ እንዲሁ እንደ ገደል ማሚቶ የሰማውን ሁሉ እየተቀበለ አብሮ ለሚጮኸው ማለቴ አይደለም፡፡ ለግብዞች አልጻፍኩም፡፡ እኔ ልጽፍ ያሰብኩና የተነሳሁ በእርግጥ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስጢርና ዘመን ምርመራ ለሚደክሙ ሰዎች መሆኑን አስቀድሜ ላንባቢዎች አመለክታለሁ፡፡”  የዘመኑ አንባቢዎችም በዚሁ አኳያ ልብ እንዲሉ አሳስባለሁ፡፡ መልካም ጊዜ!!


Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ከወራት በፊት የሆነ ነገር ነው… አንድ ወዳጃችን የሆነ ዘመዱ እንትናዬውን ስለተነጠቀ በሽቆ የሚይዘው የሚጨብጠው አጥቶ ነበር፡፡ (የዘመኑ ልጆች ቢሆኑ… “መነጣጠቅ ብርቅ ሆኖበት ነው እንዴ!” ብለው ‘ሙድ ይይዙበት’ ነበር፡፡)
ለካላችሁ በጣም ያበሸቀው…አለ አይደል…ነጣቂ የተባለው ሰው ‘የማይገፉት ዋርካ’ ቢጤ ኖሯል። ልጄ…የእኔ ቢጤ ቢሆን ኖሮ… “ሁለተኛ አጠገቧ ብትደርስ ሦስት ቀን ክፍቱን ያደረ አብሲት ነው የማደርግህ!” ብሎ ‘ቴረር’ መልቀቅ ይቻላል፡፡
ስሙኝማ…አሁን አሁን እኮ ‘ነጻ ዝውውር’ አይሉት፣ ‘የስውር ድርድር’ አይሉት… የእንትናና የእንትናዬ ቡድን የመለዋወጥ ‘የዝውውር መስኮት’ ዓመቱን ሙሉ ክፍት አይደል እንዴ!  
እኔ የምለው…ዘንድሮ ስንቱ ‘በማይገፉ ዋርካዎች’ እየተነጠቀ… “ለጣይም ፈንጋይ አለ…” እያለ አጨብጭቦ ቀርቶ የለ!
ሀሳብ አለን…የተነጠቃችሁ ሰዎች…ለእንትናዬዎቻችሁ የ‘ቫለንታይን ዴይ’ ጽጌረዳ ላኩላቸው፡፡ አሀ…ልክ ነዋ! ሰሞኑን ሚዲያ ላይ ስንማ እንደከረምነው ከሆነ…ይሄ ቫለንታይን ዴይ የሚባለው ነገር… “የመቃብሬን አፈር እንዳትረግጥ/እንዳትረግጭ…” የተባባሉ ሁሉ መልሰው የሚገናኙበት ይመስላላ!
ይቺን እውነተኛ ታሪክ ስሙኝማ…ልጅዬው አሥራ ዘጠኝ ዓመቱ ነው አሉ፡፡ እናማ… እንትንዬውን ለማስደሰት ከታወቀ የጌጣ ጌጥ መደብር እጅግ ውድ የሆነ የእጅ አምባር ይገዛል፡፡ የመደብሩ ባለቤትም… “የፍቅረኛህ ስም እላዩ ላይ እንዲቀረፅልህ ትፈልጋለህ?” ይለዋል፡፡ እሱዬውም ትንሽ አሰበና… “አልፈልግም…” ይላል፡፡ የመደብሩ ባለቤትም ምክንያቱን ይጠይቀዋል፡፡ ልጁ ምን ቢል ጥሩ ነው…“ድንገት ከእሷ ጋር ከተጣላን ለአዲሷ ገርል ፍሬንዴ እጠቀምበታለሁ…” ብሎ አረፈው፡፡ አሪፍ አይደል…ወጪ ቆጣቢ ነዋ!
በነገራችን ላይ ቀኑን ከብዙ አሥርት ዓመታት በፊት ጀምረው ሲያከብሩ የነበሩት ሰዎች እንኳን በቫለንታይን ዴይ አጀማመር ላይ ገና እየተጨቃጨቁ ነው፡፡ አንዳንዶቹ… የነጋዴዎች ቢዙ ማሟሟቂያ ነው ይላሉ፡፡ እንደውም በድሮ ጊዜ በነበረ የመልካም ምኞት መግለጫ ካርድ አምራች ኩባንያ የተፈጠረ ነው የሚሉት ነገር አለ፡፡ ይቺ እንኳን ትንሽ ታስቸግራለች…
ስሙኝማ…ስለ ‘ቫለንታይን ዴይ’ ሲያወሩ…አለ አይደል…በየአገሩ የሚቃወሙት እንዳሉ መግለጽ አሪፍ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ባል ቁጭ ብሎ መጽሐፉን ያነባል፡፡ ሚስት ቅልጥ ያለ እንቅልፏን እየለጠጠች ነበር፡፡ ለካስ ህልም ስታይ ነበር፡፡ ታዲያላችሁ… ከእንቅልፏ ስትነሳ ለባሏ
“ምን የመሰለ ህልም አየሁ መሰለህ!...” ትለዋለች።
ባልም… “ምን አይነት ህልም አየሽ…” ይላታል፡፡
እሷም ምን ትለዋለች… “በ‘ቫለንታይን ዴይ’ የዕንቁ ሀብል ስትሰጠኝ አየሁ፡፡ ትርጉሙ ምን ይመስልሀል?”
እሱዬውም… “ዛሬ ማታ መልሱን ታውቂዋለሽ…” ይላታል፡፡
እናላችሁ…ባል ሆዬ ማታ ቤቱ ሲመጣ በአሪፍ ወረቀት የተጠቀለለ ስጦታ ይዟል፡፡ “የ‘ቫለንታይን ዴይ’ ስጦታዬ ይኸው…” ብሎ ይሰጣታል፡፡ እሷም ትጠመጠምበታለች፡፡
“እኔ አላምንም! ምንድነው ያመጣህልኝ?”
“ከፍተሽ እዪው…”
እሷዬዋ እንደ ዋንጫ ልቅለቃም፣ እንደ ትከሻ እንቅጥቅጥም እየሞከራት…  የስጦታ ጥቅሉን ትከፍተዋለች፡ እናላችሁ…  ምን ብታገኝ ጥሩ ነው… ‘የህልም ፍቺ’ የሚል መጽሀፍ! ልክ ነዋ… የህልሙን ትርጉም ጠየቀችው እንጂ ሀብል ግዛልኝ አላለችውማ!
እንትናዬዎች… “በህልሜ ቪትዝ መኪና ስነዳ አየሁ፣ ትርጉሙ ምን ይመስልሀል?”   “በህልሜ ሦስት መኝታ ቤት ኮንዶሚነየም ስትከራይልኝ አየሁ፣ (ቂ…ቂ…ቂ…) ምን ማለት ነው?” እያላችሁ ዙሪያ ጥምጥም አትሂዱ፡፡ በቃ ፊት ለፊት… “ቪትዝ የማትገዛልኝ ከሆነ በኋላ ማሪኝ ብዬሻለሁ እሞትብሻለሁ..ምናምን ብትለኝ የሚሰማህ አታገኝም፡፡” “ሦስት መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም ካልተከራየህልኝ ከእንግዲህ ከአንተ ጋር መንደር፣ ለመንደር አልጓተትም፡፡ እንዴ እየጎተትከኝ የምትዞረው የልዋጭ ዕቃ መሰልኩህ!” (ቂ…ቂ…ቂ…) እያላችሁ ዕቅጩን መናገር ነው፡፡
ለነገሩ ዘንድሮ ወንዱ ሁሉ “…ግዛልኝ…” እስኪባል ሳይጠብቅ መኪና እየገዛና ኮንዶሚኒየም እየተከራየ…ድፍኑን ዓመት ‘ቫለንታይን ዴይ’ ነገር አድርጎታል ይባላል፡፡ የምር ግን… የኮንደሚኒየም ኪራይ እኮ ዝም ብሎ እዚያ ላይ አልተሰቀለም!
ስሙኝማ…ይሄ ኮንዶሚኒየም እየተከራዩ…አለ አይደል…‘ማስቀመጥ’ የምር የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት ልንጠይቅበት ይገባል፡፡ (“ጎተራ ኮንዶሚኒየም ሰው ልጠይቅ ነው…” “ብርጭቆ ኮንዶሚነየም ድረስ ብዬ መጣሁ…” ምናምን የምትሉ ወዳጆቻችን…በቃ ጠረጠርናችሁ፡፡ (እንትና…ማንም ሰው “ገንዘብ አታስቀምጥና እንትናዬዎች አስቀምጥ!” ብሎህ አያውቅም!)
እኔ የምለው…ምድረ ‘ሌጣ’ ዛሬ ማታ…ጉልበትህን አቅፈህ ተኛ፡፡
እኔ የምለው…እግር መንገዴን…‘ቫለንታይን ዴይ’ እኮ… አለ አይደል… ብዙ አገሮችም ተቃውሞዎች አሉበት፡፡ ለምሳሌ… ያለፈው ዓመት ቀኝ አክራሪ ሂንዱዎች ‘ቫለንታይን ዴይ’ ለማክበር የተሰበሰቡ ጥንዶችን በቲማቲም ወግረዋቸዋል ተብሏል፡፡ በፓኪስታንና በሌሎች አገሮችም… አለ አይደል… “ከባህላችን ውጪ ነው…” “ከእምነታችን ውጪ ነው…” በሚሉና በሌሎች ምክንያቶች ችግሮች ነበሩ።
ይሄን ዘመን ‘ቢዙም’ ተጧጡፏል፡ እኔ የምለው…‘ቫለንታይን ዴይ’ በቃ የቺስታ’ በዓል አይደለም፤ ልጄ…አንዷ ጽጌረዳ የምትገዛበት እኮ የወር የነጭ ሽንኩርት በጀትን ይይዛል፡፡ የይምር…ይቺን ሰሞን የአበባ ነጋዴ መሆን ነበር፡፡ አሀ…የዓመት በጀት ይዘጋላ! ልጄ ኑሮ ራሱ ‘ደም ብዛት’ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ልክ ነዋ…ሁለቱም ራስ ላይ ወጥተው አይደል መከራችንን የሚያሳዩን! ታዲያማ…የአሥራ አምስት ቀን የአበባ ነጋዴ ሆኖ የአሥራ አምስት ወር ፈራንካ ገቢ ማድረግ ነበር! ቢያንስ..ቲማቲም በወጣ ቁጥር ‘ደሙ’ በእኩል ፍጥነት አብሮ አይወጣም ነበር!
ስሙኝማ…እንግዲሀ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ‘ቫለንታይን ዴይ’ን…  ልክ ከአጼ እከሌ ዘመን ጀምሮ ይዘን የመጣነው በዓል ሊያስመስሉት ሲሞክሩ ትሰማላችሁ፡፡ እንግዲህ ይከበር ከተባለ… በቃ ምን ይደረጋል ይከበር…ግን ከምስረታው ጀምሮ የእኛ ያልነበረ ነገርን… አለ አይደል… በዚህ፣ በዛ ብሎ ‘የታሪካችን አካል’ አይነት ነገር ለማድረግ መሞከሩ አሪፍ ነገር አይደለም፡፡
በውጪም ዓለም ቢሆን…‘ቫለንታይን ዴይ’ በዋነኛነት የቢዙ ቀን ነው፡፡ እንደውም “ዘ ቫለንታይን ዴይ” ኢንደስትሪ የሚሉት አገላላጽ አላቸው፡፡
እናላችሁ…እኛ ዘንድም ቢሆን አሁን “ዘ ቫለንታይን ዴይ ኢንደስትሪ” የሚል እየተፈጠረ ነው። ይህ ሁሉ ‘የሚዲያ ሽፋን’ በዋነኛነት የ‘ቢዙ’ ጉዳይ ነው፡፡ ከሁለት ሳምንታት ቀድሞ ወሬ የሚሞቅለት የትኛው በዓላችን ነው! የእኛ አገር የበዓል ‘ቢዙ’ በጉና ዶሮው ላይ ነዋ!
ስሙኝማ…ይህ ‘ቫለንታይን ዴይ’ የሚባለው ነገር የፍቅረኞች ቀን ነው አይደል የሚባለው! ሀሳብ አለን… እዚህ አገር ‘ፍቅረኞች’ የሚለው ቃል ትርጉም ግራ የሚያጋባበት ዘመን ላይ ስለተደረሰ መጀመሪያ በትርጉሙ እንስማማማ! ልክ ነዋ…ፍቅርና ‘እነሆ በረከት’ እየተምታታ ነዋ!
ደግሞላችሁ…የ‘ቫለንታይን ዴይ’ በዓል ‘ተቋዳሽ’ ለመሆን ፈራንክ ያስፈልጋል፡፣ እውነቱ ይኸው ነው፡፡ እናማ…በቃ፣ “ከሌለህ የለህም…” ነው፡፡ ጥያቄ አለን…በ‘ቫለንታይን ዴይ’ አከባበር እኛም እንድንሳተፍበት ቄጤማ ተጎዝጉዞ የሚከበርበት ዘዴ ይፈጠርልን። ልክ ነዋ…ለስጦታ እንደሁ ለእንትናዬዋ… አለ አይደል… ፈንዲሻ ዘገን አድርጎ… “ለአንቺ ያለኝን ፍቅር በዚህ በእፍኝ ፈንዲሻ ስጦታ ለመግለጽ እወዳለሁ…” ምናምን ብሎ ዲስኩር ቢጤ ማድረግ፡፡
እናላችሁ… ‘ቫለንታይን ዴይ’ን መኮረጃችን ካልቀረ ቄጤማና ፈንዲሻ ታሳቢ ይሁኑልንማ! ተበድረንም ቢሆን አናጣቸውማ!
ታዲያላችሁ…ከዕለታት አንድ ቀን… ‘ጁላይ ፎርን’ ኮርጀን የምናከብር ከሆነ፣ ቄጤማና ፈንዲሻ… ‘የበዓሉ አካላት’ የሚሆኑበት ዘዴ ይፈጠርልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

     ዐርብ ታህሣሥ 3 ቀን 2007 ዓ.ም የመጀመሪያው የካይሮ ልዑካን ስብሰባ ተካሄደ፡፡ የመጀመሪያው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስብሰባ መሆኑ ነው፡፡ የስብሰባው መሠረታዊ ጉዳይ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የዐባይ ግድብን በተመለከተ ዕምነት ማስረፅ ነው (Building Trust እንደማለት) ይህን ዕምነት ማስረፅ ማለት የአገራችንን ትልቅ ስዕል (The Bigger Image) ለግብፅ ማሳወቅ ነው፡፡ ከምሁራን፣ ከኪነጥበብ ሰዎች፣ ከአትሌቶች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከምክር ቤት … ወዘተ የተውጣጡ፣ ሰዎች ናቸው ያየሁዋቸው የስብሰባው ተካፋዮች፡፡
በስብሰባው እንደስትራቴጂ የተቀመጡት መሠረተ ጉዳዮች፤
በዓይነቱ የመጀመሪያው መሆኑ
ስብሰባው የተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስብስባ መሆኑ፡፡ በሌላ ቋንቋ ህዝብ ለህዝብ መሆኑ፤
አቅጣጫው ቋሚ መሆኑ
የግብፅ አካላት በተናጠል እንዳያገኙን የአንድነት መንፈስን ማስረፅ መፈለጉ፤
ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሀሳብ ለግብፅ ሚዲያ ማሳወቅ
ከግብፅ ጋር ሳይንሳዊ፣ ኪነጥበባዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ግንኙነት አለን፡፡ ከግድቡ ባሻገር እነዚህ ሁሉ ዕሴቶች የግንኙነታችን መሠረቶች መሆናቸውን መግለፅና የጋራ ተጠቃሚነት ዋና ነገር ስለ መሆኑ፤ ወጣቶችን ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ህብረተሰቡ ያልደረሰውን መረጃ መስጠት፤ ፖሊሲውን ተግባራዊ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ግብፆች ተጨማሪ ሥራ እንዲሰሩ ማድረግ፤ audacity ልበ - ሙሉነት እና Credibility (ከነሙሉ ማዕረጉ ተቀባይነትን ማግኘትን) መፍጠር፤ በስብሰባው የተነሱ ሲሆን፤ ዋናው ቁምነገር ግን፤
ከ60ው ልዑካን መካከል ማን በወኪልነት እንደኮሚቴ ያገልግል? የሚለው ነበር፡፡
በመጀመሪያ የተነሳው ሃሳብ ከየተቋም ዘርፉ አንድ አንድ ተወካይ ተመርጦ ኮሚቴው ቢመሠረት የሚለው ሀሳብ ነበር፡፡ በኋላ ግን ወደ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ መጣን፡፡ ይኸውም፤
ከ60ዎቻችን መካከል በካይሮው ጉባዔ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጡ የሚችሉ፤ በየስብሰባው ላይ የእኛን (የሀገራችንን) ሃሳብ የሚያቀርቡ፤ ብስለትና በጉዳዩ ላይ ዕውቀት አላቸው የምንላቸውን ምርጥ 5 ሰዎች እንድንወክል፤ እነዚህም ከ10 ተጠቋሚዎች መካከል እንዲሆኑ ተስማማን፡፡
የዓርብ ከፍተኛ ቁምነገር ለእኔ ይሄ ነው! ከተጠቆሙት ሰዎች መካከል የሪፖርተሩ አማረ አረጋዊ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዋ ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም፤ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ሜትር ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን፣ ወ/ሮ መዓዛ ብሩ፣ ልዑል በዕደማርያም መኰንንን ጨምሮ ሌሎች አራት ሰዎች ያሉበት ቡድን ነው፡፡
እዚህ ላይ በጣም ሊሰመርበት የሚገባ፣ ቢያንስ እኔ እንዳስተዋልኩት፣ የአመራረጡ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ወዳጆቼ “60ዎቹ ልዑካን እንዴት እኛን ይወክላሉ?” ይሉኛል፡፡
አንድ ጊዜ ከገጣሚ ሰለሞን ዴሬሳ ጋር ስለ ኢትዮጵያ ነገር ስንወያይ፤ ከሀገራችን ቴሌቪዥንና ከየአደባባዩ ብርሃን (Lime - Light) የማይለዩ አያሌ የታይታ ሰዎችን ጠቅሼ “ምን ብናደርግ ይሻላል? በጣም አሰልቺ የሆኑ ‹ታዋቂ ሰዎች› አሉ፡፡ በእናንተም ጊዜ ነበሩ?” አልኩት፡፡ ሰለሞን የመለሰልኝ መልስ እስከዛሬ ይገርመኛል፡፡ ለብዙ ሰዎችም ነግሬአለሁ፡፡ ሰለሞን ያለኝ የሚከተለውን ነው “ነቢይ፤ ተዋቸው፡፡ ያለ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያ ሙሉ አትሆንም!” ለብዙ ጊዜ እንዳስብበት ያደረገኝ ሃሳብ ነው፡፡ ዕውነትም ኢትዮጵያ በአስተዋዮች፣ በምሁራን፣ በተጠበቡና በረቀቁ ሰዎች ብቻ ትወከል የሚለው ሃሳብ ቢያንስ ሁሉም ሰው የየራሱ አድናቂ (Fan) እንዳለው መርሳት መሆኑን ተገነዘብኩ፡፡ በየራሳቸው ዙሪያ የየራሳቸው ዋጋ ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን መቀበል አንድ ነገር ነው፡፡
ሌላው ዋና ቁም ነገር ግን፤ ከ60ዎቹ መካከል እንደ አንኳር ቡድን ማንን መረጥን? የተመረጡትስ ሰዎች ተልዕኳቸውን በማሳካት ረገድ ምን ያህል አገራዊ ፋይዳ ያለው ተግባር ያከናውናሉ? የሚለው ነው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናትን ሳይቀር ያስደመመ ታላቅ ዲፕሊማሲያዊ ተግባር የተከናወነ ይመስለኛል፡፡ ለእኔ የዚህ ምክኑ አንድና አንድ ነው፡፡ ሁሉም በየቤቱ ለሀገሩ ያለው ፍቅር፣ ሀገራዊ ኃላፊነትና ጥንቃቄ፤ ማንም ሳያዘውና፣ ሃይ ሳይለው የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር መሆኑ ነው፡፡ የማይታበል ሃቅ! “ኤጭ አይባል የአገር ጉዳይ” እንዲሉ!
በኦፊሴላዊ ሰነዱ ላይ የተመለከተውን፤ እንደመነሻ ብናየው፤ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከደራሲያን፣ ከአትሌቶች፣ ከጋዜጠኞች፣ ከኪነጥበብ ሰዎች፣ ከፖለቲካ ሰዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከምክር ቤት የመጡ ተወካዮች ናቸው የልዑካኑ አባላት፡፡ በከፊል ለማስታወስ የሚከተሉትን ስሞች ልዘርዝር፡-

የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑካን
የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ
የተከበሩ መሀመድ ረሺድ ሐጂ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ - ጉባዔ
ሜትር ሎሬት ዶክተር ጥበቡ የማነብርሃን
ሼክ ኪያር መሀመድ አማን፣ የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ም/ቤት ፕሬዚዳንት
አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል
ብፁዕ ሐጐስ ሃይሽ ፍሱህ
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ
ዶ/ር ኃይለሚካኤል አበራ
ዶ/ር አረጋ ይርዳው
ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ
ዶ/ር አባቡ ምንዳ
ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም
የተከበሩ ተስፋዬ ዳባ
የተከበሩ አቶ ሙደር ሙዘይን
የተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉ
ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን
አቶ ጥላሁን ደረሰ
አቶ ውብሸት ወርቅ - አለማየሁ
ወ/ሮ ሃያት መሀመድ
ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን
ወ/ሮ የምወድሽ በቀለ
አቶ ሙሼ ሰሙ
አቶ ጌታቸው በለጠ
ወ/ሮ መዐዛ ብሩ
አትሌት ደራርቱ ቱሉ
አቶ አማረ አረጋዊ
ወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱ
አርቲስት ጌትነት እንየው
አቶ ሠራዊት ፍቅሬ
አርቲስት ደበሽ ተመስገን
አቶ በዕደ ማርያም መኰንን
አቶ ሣምሶን ማሞ
ጨምዴሳ ኩሳ
መልካሙ ታደሰ
ተውፊቅ መደድ
መሠረት ተስፋዬ
አቶ ተስፋዬ ሽመልስ
የዓርቡ ስብሰባ ወደ ሰኞ ተሸጋገረ፡፡ የሰኞው ጠዋት ስብሰባ በዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የሚመራ ነው፡፡ ዓላማው ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎችን፣ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን ታጥቀን እንድንሄድ ነው፡፡ እግረ መንገዳችንን በኢንጂነር ስመኝ ስለህዳሴው ግድብ ጂኦግራፊያዊ ምስል፣ አቅምና ፋይዳ ገለፃ ተደርጓል፡፡ ካይሮ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች ግምትም ተተንብዮአል፡፡ ስብሰባው ምሣን የጨመረና ሎጂስቲክስን ያካተተ ነበር፡፡ እንግዲህ ማታ በራሪዎች ነን ወደ ካይሮ! ዐባይን በካይሮ በኩል ልናየው ነው!
የአምባሳደር መሀመድ ድሪር ደብዳቤ ካይሮ ጠበቀን፡፡ የሚከተለውን ይላል፡፡
ታህሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም
በካይሮ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ የኢትዮጵያ ህዝብ - ለህዝብ የዲፕሎማሲ ልዑካን አባላት እንኳን ወደ ምድረ - ግብጽ በሰላም መጣችሁ እያለ፣ ተልዕኳችሁ የተሳካ እንዲሆን ልባዊ ምኞቱን ይገልፃል፡፡
ይህ አሁን እናንተ የምታደርጉት የአጸፋ ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ከማጠናከር አንፃር የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚል ዕምነት አለን።
ኤምባሲው ከግብፅ ወገን ጋር በምታደርጓቸው ግንኙነቶች ሁሉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ከጐናችሁ እንደሚሆን ስንገልጽ በታላቅ ደስታ ነው፡፡
አምባሳደር መሀመድ ድሪር
(ይቀጥላል)

Published in ህብረተሰብ

የተከበሩ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በጥርስ ህክምናው ዘርፍ የተሠማሩ ባለሀብት ሲሆኑ በ2002 ምርጫ ተወዳድረው በማሸነፍ በፓርላማ ብቸኛ የግል እጩ ሆነዋል፡፡ ዶ/ር አሸብር በፓን አፍሪካ ፓርላማ ውስጥ በም/ፕሬዚዳንትነት እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡ በግንቦቱ ምርጫ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርገዋል፡፡

በግንቦቱ ምርጫ በእጩነት ይወዳደራሉ?
በምርጫው ለመወዳደር ጓደኞቼ ፊርማ አሰባስበውልኝ ለቦርዱ አስገብተናል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ተወዳዳሪነቴን የማረጋግጠው የእጩነት ደብተሬን ስወስድ ነው፡፡ ከእኔ  የሚጠበቀውን ሁሉ   አድርጌያለሁ፡፡
የት ነው የሚወዳደሩት?
በከፋ ዞን፣ ቦንጋ ዲንቦ ጓታ ምርጫ ጣቢያ ነው የምወዳደረው፡፡
የግል ተወዳዳሪ የመሆን ጥቅሞችና ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
አብዛኛው ጊዜ ፓርቲዎች ሚዲያ ተጠቅመው ራሳቸውን የማስተዋወቅ እድል አላቸው። ቴሌቪዥን፣ ራዲዮ ይጠቀማሉ፤ ለምርጫው ከመንግስት በጀት ያገኛሉ፡፡ ለግል ተወዳዳሪዎች ግን እነዚህ ሁሉ የሉም፡፡ እኛ የግል ተወዳዳሪዎች በራሳችን ወጪ መቀስቀስ፣ በራሳችን የቅስቀሳ አውታር መጠቀም ስለሚጠበቅብን ብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያለነው፡፡ አንድ ግለሰብ ለመወዳደር ሲፈልግ፣ በዚህ ደረጃ ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡
ጥቅሞቹስ?
ራሱ ኢህአዴግን ብትወስድ አባላቱ ከ10 ሚሊዮን አይበልጡም፡፡ ከህዝቡ 70 እና 80 በመቶው የፓርቲ አባል አይደለም ማለት ነው። ስለዚህ ህዝቡ እኛን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ከየትኛውም ፓርቲ ገለልተኛ መሆን ለአስተያየትም ለፍርድም ይጠቅማል፡፡ ብዙ ሰው ወደ ፓርቲ አይጠጋም፤ለዚህም ምክንያቱ ገለልተኛ መሆን ስለሚፈልግ ነው፡፡
የግል ተወዳዳሪ መሆን ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ግለሰቡ ራሱ በራሱ ነው ወሳኝ የሚሆነው፡፡ የፓርቲ ዲሲፒሊን ተብሎ የሚገዛበት ነገር አይኖርም፡፡ የምታስበውን ያመንከውን ትናገራለህ፤ታደርጋለህ። የፓርቲ ፕሮግራም ነው በሚል ያላመንክበትን በብዙኃኑ ተገዝተህ እንድታምን አይሆንም፡፡ ራስን ብቻ ነው የሚኮነው፡፡ ህዝቡም ራሱን ሆኖ የሚቀርብ  ይፈልጋል፡፡
 የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል? በምርጫው ውጤት ያገኛሉ ብለው ይገምታሉ?
በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ህዝቡ ያገባኛል፣ የራሴ ጉዳይ ነው በሚል በስፋት ወጥቶ ድምፅ የሰጠው በምርጫ 97 ነው፡፡ ያኔ ህዝብ ለውጥ ማየት አለብኝ፣ ብሎ በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለተቃዋሚዎች ሙሉ ድምፅ ሰጥቶ አሸንፈው ነበር። ሆኖም አስተዳደሩን አለመረከባቸው ዛሬ ገዥው ፓርቲ አብላጫውን ስልጣን እንዲቆጣጠር አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ አዲስ አበባ ማለት ከአንድ አገር በላይ ነው፡፡ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም ተቋማት መቀመጫ ነው፡፡ አዲስ አበባን መያዝ ማለት ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው፡፡ ያንን ይዘው ቢሆን ኖሮ ኢህአዴግ ዛሬ አውራ ፓርቲ አይሆንም  ነበር፡፡ አዲስ አበባ መሪ ስታጣ ህዝቡ፣ “ለካ ሊያስተዳድሩኝ አይችሉም” አለ፡፡ ገዥውም ፓርቲ ግለ ሂስ አድረገና ህዝቡም ተቀበለው፡፡ ከዚያ በኋላ ገዢው ፓርቲ ልማትን፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ለመመረጥ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የኛ ተቃዋሚዎች መኖራቸውን የምንሰማው፣ አሁን ለመመረጥ ሲሯሯጡ ነው፡፡ ይሄ በቂ አይደለም፡፡ በአንድና ሁለት ወር ውስጥ ምን አቅርበው ሊመረጡ ነው? ይሄ ለህዝቡም ፈተና ነው የሚሆነው፡፡ ውጤቱን እንግዲህ ሲደርስ እናየዋለን፡፡
እርስዎስ  በምርጫው አሸንፈው ለሁለተኛ ጊዜ ፓርላማ የሚገቡ ይመስልዎታል?
ፓርላማ እንደምገባ አልጠራጠርም፡፡ ተመልሼ እመረጣለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኔ ከራሴ ህዝብ ጋር ነው የቆየሁትም፡፡ በፊት ሳያውቀኝ የመረጠኝ አሁን መልዕክተኛወ ሆኜ የላከኝን ፈፃሚ መሆኔን ከመቼውም በበለጠ ያውቃል፡፡ ስለዚህ እመረጣለሁ ብዬ በእርግጠኝነት  መናገር እችላለሁ፡፡ በእርግጥ የምወዳደረው ከኢህአዴግም ከተቃዋሚዎችም ጋር ነው፡፡ እኔ ከዚህ በፊት ም/ቤት ስገባ ኢህአዴግን እንደማልቃወም፣ ገብቼም የኢህአዴግ ደጋፊ እንደምሆን ቃል ገብቼ ነው የተመረጥኩት፡፡ በእርግጥም አንድም ቀን ኢህአዴግን ተቃውሜ አላውቅም፡፡ በዚህ የተነሳ የገዥው ፓርቲ አባል ከእኔ ጋር ይወዳደራል ብዬ አልጠበቅሁም  ነበር፡፡ እኔ እኮ የአባሉን ያህል ስሰራ ነው የቆየሁት፤ ሃገርን ወክዬ በፓን አፍሪካ ፓርላማ የተቀመጥኩ ሰው ነኛ። ይሄ የፓን አፍሪካ ፓርላማ ቦታችንን ማስጠበቅ የምንችለውም እኔ በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ ስኖር ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይሄንንም ከግምት ውስጥ የሚያስገባ መስሎኝ ነበር፡፡
 አሁን ስማቸውን የማልጠቅሳቸው ኃላፊ፣ ከኔ ጋር እንደማይወዳደሩ ሲናገሩ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ መወዳደሩ የገቡ ይመስለኛል፡፡ እኔ እንደገና ተመርጬ ፓርላማ ብገባም ኢህአዴግን አልቃወምም፡፡ በእኔ እምነት ኢህአዴግ ለሃገሪቱም ለህዝቡም ጥሩ ስራዎች ሰርቷል፡፡ ከዚህ አንጻር የእኔ ፓርላማ መግባት ድሮም አልረበሸውም፣ አሁንም የሚረብሸው አይመስለኝም፡፡ በፓን አፍሪካ ፓርላማ ኢትዮጵያ ያላትን ቦታ ለማስጠበቅ ያስችለኛል ብዬ ስለማስብ ነው ወደዚህ ምርጫ የገባሁት፡፡
ኢህአዴግን የማይቃወሙና በፖሊሲው የሚስማሙ ከሆነ ለምን አባል አይሆኑም?
ይሄን እኔን ከመጠየቅ ኢህአዴግን መጠየቅ ይቀላል፡፡ “ለምን ዶ/ር አሸብርን አባል አታደርገውም?”ተብሎ ቢጠየቅ፣ኢህአዴግ የራሱን መልስ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እኔ ግን ኢህአዴግን ተቃውሜም አላውቅ፣ልቃወምም አልችልም፡፡ በእኔ እምነት ኢህአዴግ የምወዳደርበትን አካባቢ ቢተውልኝ የሚጐዳው ነገር አይኖርም፡፡ አሁን ከሚተነበየው አንጻር፣ኢህአዴግ በሰፊው ሊያሸንፍ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ከዚህ በፊትም ኢህአዴጎች ለእነ አቶ በትሩ አደም ለቀውላቸው የተመረጡበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን ሠርተው የዚህ አይነት እውቅና እንዳገኙ ባላውቅም፣ እኔ እንደ አንድ ዜጋ ራሴን ሳስብ ግን የሚጠበቅብኝን ሰርቻለሁ። እውቅና መስጠት የዚያኛው ወገን ጉዳይ ነው፡፡ “ለምን አባል አልሆንክም?” ለሚለው፣ እነሱ ምን ዓይነት ሰው አባል እንደሚያደርጉ መጠየቁ የሚቀል ይመስለኛል፡፡
እርስዎ አባል የመሆን ፍላጎት አለዎት?
መጀመሪያ መታወቅ ያለበት የእነሱ ፍላጎት ነው። ማንን አባል እንደሚያደርጉ ከእነሱ ማወቅ ይቀላል። እኔ በበኩሌ፣ የፓርቲ አባል ባልሆን ለራሴም ለሌላውም እጠቅማለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ብትሆንም የሚጎዳ ነገር የለውም፡፡

“...ትዳር ከያዝኩኝ ከአስራ ሁለት አመት በሁዋላ ነበር ያረገዝኩት፡፡ እርግዝናው ከመከሰቱ

አስቀድሞ በእኔም ይሁን በባለቤቴ ቤተሰቦች ዘንድ የተመሳሰለ ቅሬታን አስተናግጃለሁ፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነበር፡፡ የእሱም ቤተሰቦች እኔን መሐን ሲሉ ...የእኔም ቤተሰቦች እሱን መሐን ሲሉ ...እጅግ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ነበር ሁለታችንንም የገጠመን፡፡ እኔ እንዲያውም ቢቸግረኝ... ባለቤቴን ...በቃ ልጅ አስወልደህ አምጣ...የሚል ፈቃድ ሰጥቼዋለሁ፡፡ እሱ ግን በምንም ምክንያት አንቺን ትቼ ሌላ ጋ አልሄድም በማለቱ ኑሮአችን በቤተሰብ ውጥረት ሲሰቃይ ቆይቶአል፡፡ በሁዋላ ግን ሕክምናው ...ጸበሉ ...የተቻለው ሁሉ ተደርጎ ሳይሳካ ከቆየ በሁዋላ እርግዝናው ሳይታሰብ ተከሰተ፡፡ እኔ እንዲያውም ሕመም ይሆናል እንጂ መቼም እርግዝና አይደለም ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ሐኪሞቹ ግን ሕመም አይደለም ...እርግዝና ነው... በማለታቸው ተደሰትን፡፡ ምን ያረጋል... ደስታው ደስታ እንደሆነ ቢዘልቅ ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡ በማህጸኔ ውስጥ ኢንፌክሽን በመኖሩ ምክንያት ጽንሱ መቀጠል ስላልቻለ እና እኔም በጣም ስለታመምኩ እርግዝናው እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡ ከምንጊዜውም በላይ እጅግ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ ከዚያም በሁዋላ ማርገዝ አልቻልኩም፡፡         ትእግስት ሺፈራው ከኮተቤየትእግስት ደብዳቤ የደረሰን በፖስታ ነበር፡፡ እኛም ገጠመኙን ይዘን ወደሕክምና ባለሙያ ነበር ያመራነው፡፡ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ በጳውሎስ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻ ሊስት በማህጸን ኢንፌክሽንና እርግዝና ዙሪያ ለዚህ እትም ማብራሪያ እንዲሰጡ  ተጋብዘዋል፡፡ ዶ/ር ታደሰ እንደሚሉት ኢንፌክሽን ሲባል መገለጫው ብዙ ነው፡፡  በሽታን ሊያመጡ የሚችሉ ተሀዋስያን መገኘት የሌለባቸው ቦታ ላይ ከተገኙ ኢንፌክሽን ወይንም መመረዝ ይከሰታል፡፡ የማህጸን ኢንፌክሽንን ለይተን ስናይ ደግሞ በተለምዶ ብዙ አይነት ሲሆን ምንጩ ባክቴሪያ፣ ፈንገስ፣ ቫይረስ ወይንም ሌሎች ፓራሳይትስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኢንፌክሽኑ ያጠቃውስ የትኛውን
የማህጸን ክፍል ነው የሚለውን መለየትም ያስፈልጋል፡፡ ኢንፌክሽኑ በታችኛው የማህጸን ክፍል ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ብዙውን ጊዜ ቀላል የሆነ ኢንፌክሽን ነው፡፡ ቀላል ሲባልም ...ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ምልክታቸውም በፍጥነት የሚታይ ነው፡፡  በታችኛው የማህጸን ክፍል የሚከሰተው ኢንፌክሽን በአብዛኛውም በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ የሚተላለፍ እንደ ጨብጥ (ጎኖሪያ) የመሳሰሉት ስለሆኑ ምልክታቸው በታየ ጊዜ ሕክምናው ስለሚሰጥ በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህም ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ምንም ችግር አያስከትሉም፡፡/ር ታደሰ እንደሚሉት የታችኛው የማህጸን ክፍል በኢንፌክሽን ተያዘ ሲባል ብዙ ጊዜ ኢንፌክሽኑ ወደላይኛው የማህጸን ክፍልም የመዛመት እድል ይኖረዋል፡፡ በዋናው ማህጸን ክፍል ወይንም በዘር መተላለፊያው እንዲሁም በዘር ፍሬ መፈጠሪያው አካባቢ ወይንም ዙሪያውን ያሉትን የሰውነት ክፍሎች የተዛመተው ኢንፌክሽን ጉዳት ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡
ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ችግር የሚፈጠረው ኢንፌክሽኑ ወደላይኛው የማህጸን ክፍል ከገባ በሁዋላ፡-
የማህጸን የውስጥ ክፍል የመቁሰል እና ጠባሳ ምልክት ሊያሳይ ይችላል፡፡የዘር መተላለፊያ ቱቦው ሊቆስልና ሊዘጋ ይችላል፡፡የዘር ፍሬ የሚመረትበት አካባቢ መግል የመቋጠርና የመያያዝ ሁኔታ ሊኖረው ይችላል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች እርግዝና እንዳይከሰት ማድረግ ወይንም እርግዝናው ቢከሰትም እንዳይቀጥል ምክንያት የመሆን አለበለዚያም ከማህጸን ውጭ እርግዝና እንዲከሰት የማድረግ አቅም አላቸው፡፡ ይህም የረጅም ጊዜ ጠንቅ ተብሎ ይገለጻል፡፡ ኢንፌክሽኑ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ጉዳት ያስከትላል ሲባል በሰውነት ክፍል ውስጥ ስለተገኘ ብቻ ሳይሆን ለመራቢያ የሚያገለግሉ የሰውነት ክፍሎች ላይ በሚያደርሱት ጉዳት ነው፡፡ የመራቢያ አካላቱ ጉዳት ደረሰባቸው ሲባልም የሰውነት የመከላከል አቅም እነዚህን በሽታ አምጪ ሕዋሳት ለማጥፋት ሲል የሚያደርገው ጦርነት  ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌም የዘር ማስተላለፊያ ቲዩብ ቆስሎ ቢገኝ  ምክንያቱ ሰውነታችን እነዚያን እየተባዙ ያሉ ጀርሞች ለማጥፋት በሚያደርገው ቁጣ የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህም በዋናነት ከኢንፌክሽኑ በላ ችግር የሚሆነው ሰውነት ተሐዋስያኑን ለማጥፋት ሲል በሚወስደው ተፈጥሮአዊ እርምጃ ሰውነት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ነው፡፡ ኢንፌክሽን ሲከሰት ጉዳት እስኪያደርስ ድረስ የተወሰነ ጊዜ ስለሚወስድ በዚህ መሀል እርግዝና ሊከሰት ይችላል፡፡ በማህጸን የታችኛው ክፍል የሚታይ ችግር ከሆነ በቀላሉ ሊታከም የሚችል ሲሆን በላይኛው የማህጸን ክፍልም ቢሆን ምልክት ሲታይ እርግዝናውም ቢኖር ሕክምናው ይሰጣል፡፡ በእርግዝና ጊዜ ማህጸን ይዘጋል... ስለሆነም ምልክቶቹን እንዴት ማየት ይቻላል?  ለሚለው ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ እንደሚሉት የተጎዳው ክፍል የታችኛው የማህጸን ክፍል ከሆነ የፈሳሽ መኖር የደም መፍሰስ የመሳሰሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላል፡፡ ኢንፌክሽኑ የደረሰው በላይኛው የማህጸን ክፍል ላይ ከሆነ ደግሞ ከፈሳሽ ይልቅ ሌሎች ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌም ትኩሳት፣ በሆድ አካባቢ ከበድ ያለ ህመም (በምርመራ ወቅት በትንሽ እንኩዋን ሲነካ ከፍተኛ ሕመም የመሰማት ሁኔታ) ይከሰታል፡፡ ከዚህም ባለፈ የላቦራቶሪ ምርመራ የመሳሰሉት ተደርገው በማህጸን ውስጥ
ኢንፌክሽን ካለ ጽንሱ እያለም ቢሆን ሕክምና ይደረጋል፡፡ በእርግጥ ሕክምናው ጠንከር ያለና
ክትትል የሚያስፈልገው ስለሚሆን ሆስፒታል እስከመተኛት የሚያደርስ ሊሆን ይችላል፡፡ የጽንሱ ሁኔታ እናትየው ሕክምናውን እየወሰደች እድገቱን ሊቀጥል ይችላል... አለበለዚይም ሕመሙ ከፍተኛ ከሆነ ሊያጨናግፈውም ይችላል፡፡ ኢንፌክሽን መኖሩ ብቻ ጽንሱን የሚያቋርጠው ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ሰውነትዋን ከመረዘው ምናልባት የሚኖር አጋጣሚ ነው፡፡ በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ የሚተላለፉት እንደ ጨብጥ፣ ቂጥኝ የመሳሰሉት ኢንፌክሽኖች በእርግዝና ወቅት ሊከሰቱ ወይንም ከእርግዝናም በፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ናቸው፡፡ እንደዚህ ያሉት ኢንፌክሽኖች እርግዝናው እንዲወርድ ምክንያት ሊሆኑ ሲችሉ ከዚህም ባለፈ ወደ ጽንሱ የመተላለፍ አቅም አላቸው፡፡ ጽንስ ሆድ ውስጥ የመቀጨጭ፣ጽንስ ሆድ ውስጥ የመጥፋት ወይንም ያለቀኑ መወለድ ወይንም... እነዚህ ሁሉ ሳይከሰቱ ቀርተው ልጅ የኢንፌክሽኑ ተጎጂ ሆኖ ሊወለድ ስለሚችል እናትየውን ቶሎ በማከም ልጁንም ማዳን ይቻላል፡፡ባለሙያው እንደሚገልጹት እርጉዝ ሴቶች እንደተገኘ ወይንም በቀላሉ መድሀኒትን አይጠቀሙም ቢባልም በአንዳንድ ምክንያቶች ግን የተለየ ሕክምና ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በጽንስ ላይ ችግር የሚያስከትሉ ...ፈጽሞ በእርግዝና ወቅት የማይወሰዱ ተብለው የተለዩ መድሀኒቶች አሉ፡፡ንስ ላይ ምናልባት ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ግን የመድሀኒቱ ጠቀሜታ ከጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል ተብሎ የሚሰጡ አሉ፡፡ ጽንስ ላይ ችግር ያምጣ አያምጣ አይታወቅም፡፡ ግን የመድሀኒቱ ጠቀሜታ ለእናትየውም ይሁን ለጽንሱ ጠቀሜታ አለው የሚባሉ መድሀኒቶች አሉ፡፡ ፈጽሞ በጽንስ ላይ ምንም ችግር አያመጡም የሚባሉ የመድሀኒት አይነቶች አሉ፡፡
ስለዚህ እነዚህ መድሀኒቶች በውል ተለይተው የሚታወቁ ሲሆን እንደሌላው መድሀኒት ዝም ተብሎ በቀላሉ የሚወሰድ ሳይሆን በሐኪሞች ልዩ ትእዛዝ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሰጡ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ያለው ግንዛቤ ከማህጸን ፈሳሽ ከታየ እንደ ኢንፌክሽን የመቁጠር ዝንባሌ ያለው ነው፡፡ ነገር ግን በተለይም በእርግዝና ወቅት በማህጸን አካባቢ ብዙ ለውጥ ያለ ሲሆን ከነዚህም አንዱ የፈሳሽ መብዛት ነው፡፡ አንዳንድ እርጉዝ ሴቶች አልፎ አልፎ ሞዴስ እስከመጠቀም የሚደርሱበት ሁኔታም ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ፈሳሽ ከኢንፌክሽን የመጣ ነው የምንለው መቼ ነው የሚለውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ መብዛቱ አንዱ ምልክት ቢሆንም ብቻውን ግን ኢንፌክሽን ነው አያሰኘውም፡፡ ከዛ ባለፈ ግን የማሳከክ ወይንም የማቃጠል ስሜት ካለው ወይንም መልኩ ከሌላ ጊዜ የተቀየረ ሲሆን ...ወዘተ ኢንፌክሽን መሆኑን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ ስለዚህም ሕክምናውን በጊዜው ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ፡፡ በስተመጨረሻም ዶ/ር ታደሰ በተለይም በእርግዝና ወቅት ከሚኖረው የአካል ገጽታ ጋር በተያያዘ የገለጹትን እናስነብባችሁ፡፡ “...አንዲት እናት ከማርገዝዋ በፊት እና በእርግዝና ላይ እያለች የሚያመሳስላት ነገር     ቢኖር ስምዋ ብቻ ነው፡፡” ለምን? የሚለውን ጥያቄ መልስ በቀጣዩ እትም እናስነብባችሁዋለን፡፡ ይቀጥላል

Published in ላንተና ላንቺ
Page 7 of 13