Saturday, 14 February 2015 13:37

የካንሰር ገዳይነት ጨምሯል

      በድሃ አገራት በየ2 ደቂቃው አንዲት ሴት በማህፀን በር ካንሰር ህይወቷ ሲያልፍ፤ በዓመት 230ሺ ሴቶች በበሽታው ይሞታሉ በካንሰር የሚሞተው በኤችአይቪ/ኤድስ ከሚሞተው በእጥፍ ይበልጣልካንሰር ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የህመም አይነቶች ጥቅል መጠሪያ ሲሆን ህመሙ የሚከሰተው የካንሰር ሴሎች ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ አድገው ጤናማ የሆኑትን ሴሎች ሲወሯቸው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ መነሻቸው የሚታወቅና በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰቱም የካንሰር ዓይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በአብዛኛው መነሻ ምክንያቱ ሲጋራ ማጨስ የሆነውን የሳንባ ካንሰርንና በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰቱትን የማህፀን በር እንዲሁም የጉበት ካንሰርን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በመላው ዓለም በየዓመቱ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል ከስምንቱ አንዱ የሞታቸው መንስኤ የካንሰር ህመም ነው፡፡ እንደ ጤና ድርጅቱ መረጃ፤ በየዓመቱ በካንሰር ህመም ሳቢያ ህይወቱን የሚያጣው ሰው በኤችአይቪ/ኤድስ ከሚሞተው በእጥፍ ይበልጣል፡፡ አለም አቀፉ የካንሰር ድርጅት በ2012 ዓ.ም ይፋ ያደረገው መረጃም፤ በዓለም በየዓመቱ 7 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ በካንሰር ህመም ሳቢያ ህይወቱ የሚያልፍ ሲሆን አስራ አንድ ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በየዓመቱ በበሽታው ይያዛል፡፡ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ከአምስት አመት በኋላ (እ.ኤ.አ በ2020) በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ሰዎች በካንሰር ህመም ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን በየዓመቱ በካንሰር በሽታ የሚያዘው ሰው ቁጥር ደግሞ 16 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአለም ካንሰር ቀንን በማስመልከት ባለፈው ረቡዕ በሒልተን ሆቴል የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱና ቀዳማይት እመቤት ሮማን ተስፋዬ በተገኙበት በተከፈተው ሲምፖዚዬም፤ የማህፀን ካንሰር ቅድመ ምርመራና ህክምናን በተመረጡ የጤና ተቋማት ለማስጀመር የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ ተደርጓል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ ንደተናገሩት፤
በአሁኑ ወቅት በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የመጠቃት ዕድላቸው እየጨመረ የመጣ ሲሆን ችግሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የጤናው ዘርፍ ፖሊሲ ክለሳ ተጀምሯል።
በአገራችን ሴቶችን ብቻ ከሚያጠቁት የካንሰር አይነቶች አንዱ የሆነውን የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግና ህክምና መስጠት የሚችሉ በርካታ የጤና ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንና በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በእያንዳንዱ ወረዳ መሰል የጤና ማዕከላትን ለማስፋፋት መታቀዱን ገልፀዋል፡፡ የካንሰር ህመም በአገሪቱ እጅግ ከፍ ያለ ጉዳት እያስከተለ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በቂ የህክምና ባለሙያዎች አለመኖራቸውና ህክምናው የሚሰጥባቸው ተቋማትና መሣሪያዎች በቂ አለመሆን
ችግሩን እንዳባባሰው ጠቁመዋል፡፡ በካንሰር ህመም ስፔሻላይዝድ ያደረጉና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች (oncologist) ሶስት ብቻ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ከሰተብርሃን፤ እነዚህ ባለሙያዎች አንድ ሰው መሥራት ከሚችለው ጊዜ በላይ የራሳቸውን ጤና አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ ያለእረፍት እየሰሩ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡  በቅርቡ የካንሰር ህክምናን ለማገዝ የሚያስችል የኬሞቴራፒ መሣሪያ በ14 ሚሊዮን ዶላር  መገዛቱንና ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለካንሰር ህመም ሕክምና የሚያገለግሉ መድሃኒቶችም ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ መድሃኒቶቹ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ሰዎች በነፃ የሚሰጥ ሲሆን መግዛት ለሚችሉት ደግሞ በ50 በመቶ ቅናሽ እንደሚሸጥ ገልፀዋል፡፡
ከእኛ አያልፍም (“Not Beyond Us”) በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚህ አገር አቀፍ ሲምፖዚየም ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ቀዳማይት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ዋንኞቹ ገዳይ በሽታዎች እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመው አገራችንም የዚህ ችግር ተጠቂ በመሆን ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል፡፡ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል ካንሰር አንዱ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ሮማን፤ በአሁኑ ወቅት በካንሰር ህመም ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱንና በተለይም የማህፀን በር ካንሰርና የመሳሰሉ በቅድሚያ መከላከል በምንችላቸው በሽታዎች ምክንያት ዜጐቻችን እየሞቱ መሆኑ የሚያሣዝን ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራና ህክምና የሚሰጡ የጤና ማዕከላት በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር አዋሣ፣ ጐንደር፣ መቀሌና ጅማ እንደሚገኙ በመጠቆምም ማዕከላቱን ለማስፋፋትና ተደራሽነታቸውን ለማረጋገጥ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ደይሬክተር ዶ/ር ማህሌት ክፍሌ ባቀረቡት ጽሑፍ በአገራችን በየዓመቱ ከሚከሰቱ ሞቶች 40 በመቶው
መንስኤያቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደሆኑ የአለም ጤና ድርጅትን የቅርብ ጊዜ ሪፖርት ዋቢ አድርገው ጠቅሰዋል፡፡ ሴቶችን ብቻ ለይተው ከሚያጠቁና በቀላል ምርመራና ህክምና ልንከላከላቸው እየቻልን እጅግ በርካታ ሴቶቻችንን ለህልፈተ ህይወት ከሚያበቁ የካንሰር አይነቶች አንዱ የሆነውን የማህፀን በር ካንሰር ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ዶ/ር ማህሌት ጠቁመዋል፡፡ International Agency for Research on Cancer (IARC) የተባለ ድርጅት በ2012 በኢትዮጵያ ባደረገው ጥናት፤ በአገሪቱ 60ሺ 749 የካንሰር ህሙማን መኖራቸውን ጠቁሞ ከእነዚህ መካከል 19ሺ654 የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ 41ሺ095 ደግሞ ሴቶች ናቸው ብሏል፡፡ የአንጀት ካንሰር ዋንኛው የወንዶች ገዳይ በሽታ መሆኑን ያመለከተው ጥናቱ፤ የጡትና የማህፀን በር ካንሰር ዋንኛው የሴቶች ገዳይ በሽታ እንደሆነ ጠቁሟል። ከኤችአይቪ/ ኤድስ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሴቶች በማህፀን በር ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከሌለባቸው ሴቶች በአምስት እጥፍ የሚበልጥ መሆኑም በሲምፖዚየሙ ላይ ተገልጿል፡፡ የሴቶች ገዳይ በሽታ እንደሆነ የሚነገርለት የማህፀን በር ካንሰር የሚከሰተው የካንሰሩ አማጭ በሆነው “ሒዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ” አማካኝነት ሲሆን በሽታው ማንኛዋንም የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የጀመረች ሴት ሊይዝ ይችላል፡፡ የአሜሪካ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ማህበር መረጃ፤ አንዲት ሴት አንደኛ ደረጃ በሚባለውና ገና በጀመረው ዓይነት የማህፀን በር ካንሰር ተይዛ ለአምስት አመት በህይወት የመቆየት እድሏ 95 በመቶ ሲሆን ካንሰሩ ካለበት የማህፀን በር አካባቢ ተሰራጭቶ ወደ ሌላ የሰውነቷ ክፍሎች ከተሰራጨ በኋላ ለአምስት አመት በህይወት የመቆየት እድሏ 10 በመቶ ብቻ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ “ፒንክ ኤንድ ሬድ ሪባን” በተባለና በማህፀን በርና ጡት ካንሰር በሽታዎች ሳቢያ የሚሞቱ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ዜጐችን ቁጥር ለመቀነስ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በሲምፖዚየሙ ላይ ፕሮግራሙን በይፋ የጀመረ ሲሆን የተለያዩ አለምአቀፍ ተቋማትም በፕሮግራሙ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡ ድርጅቱ በዕለቱ ይፋ ያደረገው መረጃ ንደሚያመለክተውም፤ በዓለም በየሁለት ደቂቃው አንዲት ሴት በማህፀን በር ካንሰር ሳቢያ ለህልፈት የምትበቃ ሲሆን በየዓመቱ ደግሞ 230 ሺ ሴቶች በዚሁ በሽታ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡

Published in ዋናው ጤና

ከዕለታት አንድ ቀን ዕመት ጦጢት ዘር ልትዘራ ወደ እርሻ ቦታ ትሄዳለች፡፡ ከዚያም በሰፊው እርሻ

ላይ በመት በመት ስትዘራ ትታያለች፡፡
በእርሻው ዳር የሚያልፈው ሰው ሁሉ ጥያቄ ይጠይቃል፡፡
ጦጢት ምን ዘራሽ?“ ይላታል አንዱ፡፡
“ዘንጋዳ” ትላለች ጦጢት፤ ኩራቷ ፊቷ ላይ እየተነበበ፡፡
“ጦጢት ምን ዘራሽ?” ይላታል ሁለተኛው፡፡
“ስንዴ!” ትላለች ጦጢት፡፡
“ጦጢት ምን ዘራሽ?” ይላታል ሌላው፡፡
“ጤፍ!” ትላለች፡፡
“ጦጢት ምን ዘራሽ?” ደሞ ሌላው፡፡
“አተር!” ትላለች፡፡
አንዳቸውም ከእጁዋ የሚወጣውን ዘር አለማየታቸው እየገረማት ነው መልስ የምትሰጠው፡፡ የመጨረሻው ሰው መጣና፣ “እሜት ጦጢት፣ ምን ዘራሽ?” አላት
“ባቄላ!” አለችው፡፡
“እንዲያው ባቄላ እዚህ መሬት ላይ ይበቅል ይመስል … ምን ይበጅሻል?
“ማምሻውን ሁኔታውን እዩ?” ብላ መለሰች፡፡ ጦጢት ስትዘራ ስትታይ ዋለችና ወደ ማታ ወደ እርሻው ተመልሳ መጣች፡፡ ከዚያም ቀን ስትዘራ የዋለችውን ዘር እንደገና ከእርሻው እያወጣች ስልቻዋ ውስጥ ትከት ጀመር፡፡ ቀን ስትዘራ ያዩዋት ሰዎች ከገበያ ሲመለሱ የምታደርገውን አይተው በመገረም፤ “እመት ጦጢት፤ ብልጥ የነበርሺው ሴትዮ አሁንስ ተጃጃልሽ መሰል! ደሞ ምን ልሁን ብለሽ ነው

የዘራሽውን መልሰሽ የምትለቅሚው?”
ጦጢትም፤
“ወዳጆቼ! ያለንበት ዘመን አያስተማምንም! የያዙትን ይዞ ወደ ቤት ክትት ነው የሚሻለው፡፡ ንብረትን በእጅ ይዞ ማደርን የመሰለ ነገር የለም!!” ብላ መለሰች፡፡
*                  *               *
በማናቸውም የህይወታችን መንገድ ጥርጣሬን ይዘን ከተጓዝን ዕቅዳችን በቅጡ አይሳካም፡፡ የምናደርገው ነገር ሁሉ ልባዊ አይሆንምና ውሽልሽል አጥር ነው የምናጥረው፡፡ ውሽልሽል አጥር ለአደጋ የተጋለጠ ነው፤ እንደጦጢት የምንዘራውን እየደበቅን መጓዝ፣ አልፈን ተርፈንም የዘራነውን መልሰን መልቀምና ይዘን ማደር ግዴታ እስኪሆን ድረስ ኑሮአችን ያልተረጋጋ ይሆናል፡፡ ያልተረጋጋ ዲሞክራሲ፣ ያልተረጋጋ  ፖለቲካን ነው የሚወልደው፡፡ ያልተረጋጋ ፖለቲካ ያልተረጋጋ ኢኮኖሚን ነው ይዞ እሚያዘግመው፡፡ የዚህ ባለቤት የሚሆነው ያልተረጋጋ ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ሲጠራጠር ደግ አይደለም፡፤ ይሄን ልብ ብሎ ማስተዋል ይጠይቃል፡፡ ሼክስፒር እንደሚነግረን፣
“ግን እንደዚሁ እንደህንፃ፣ ላዩ በሰም አንፀባርቆ
አካባቢው በጌጥ ደምቆ
መሰረቱ ግን በግድፈት፣ በአገም ጠቀም ተደባብቆ
በመሀንዲስ ጥበብ ጉድለት፣ ወይ ባጉል መራቀቅ ዘፍቆ
ከስህተቱም ከጥራቱም፣ ተቻችሎ አለ ተጣብቆ፡፡
እንግዲህ  ሐምሌት ምናልባት፣ ዛሬ እወድሻለሁ ሲል
በፍቅሩ የልብ ጥራት፣ አይገኝ ይሆናል እክል
ግን የልደቱን ደረጃ፣ ስታስቢው ደሙን ቅጅ
ፍቃዱ የሱ እንዳልሆነ፣ አስተውይ የእናቴ ልጅ፡፡”
ሌላው አስጊና አትጊ ነገር እርስ በርስ መጠራጠር ነው፡፡ መሪዎች ካልተማመኑ ተመሪዎች ተግባብተው መራመድ ይቸግራቸዋል፡፡ ተግባብተው የማይራመዱ ሰዎች ወንዝ ለወንዝ ሲማማሉ ነው የሚኖሩት፡፡
“ዕምነት ሲታመምሺ ወረቀት መፈራረም” ይለዋል ጸጋዬ ገ/መድህን፡፡ ቢሮክራሲያችን፣ ፓርቲዎቻችንም፣
አመራሮቻችንም ከአበሻ የጥርጣሬ ድርና ማግ ነው ተሰሩት፡፡ ዛሬ የተባለው ነገ የሚሻረው ለዚህ ነው፡፡
እኔ ከሁሉ በላይ ነኝ የሚል አስተሳሰብ አጥፊ ነው፡፡ የበላይነትን በተሻለ ሥራ ካላሳየን ከፉከራ አያልፍም፡፡
“የተሻልን ነን እያልን
ያልተሻለ ነገር ከሰራን
መሻላችን ምኑ ላይ ነው፣ ትላንት ላይ ከተጋደምን”እንደሚለው ነው ገጣሚው፡፡
ህዝብ መንግስትን አምኖ በራሱ ተነሳሽነት ካልተንቀሳቀሰ፣ ዲሞክራሲው ጤነኛ ነወይ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ የምስራቅ አውሮፓ መንግስታት ብትንትናቸው እስኪወጣ ድረስ 98 በመቶ ምርጫውን አሸንፈናል ይሉ እንደነበር አለመርሳት ብልህነት ነው፡፡ ያልመረጠው ለምን እንዳልተመረጠ ብቻ ሳይሆን የመረጠው ለምን እንደሆነ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ ቀስቅሰን፣ አስገድደን ወይ አታለን መመረጥ ጭብጨባን እንጂ ልባዊ ድጋፍን አያስገኝም፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ጸሀፍት፤ “ገባው አልገባው አይደለም የፖለቲካ ሚስጥሩ፡፡ ተቀበለ አልተቀበለ  ነው እንጂ” ይላሉ፡፡ ሆኖም ጊዜያዊ ነው፡፡ እንደሚታወቀው እንኳን ፖለቲካው ታሪክም አሸናፊዎች የሚፅፉት ተረት ነው፤ ይሏል፡፡ ስለዚህም ኢ-ተዓማኒ ሪፖርት በተነገረ ቁጥር፣ ሙገሳና የአፍ ሙካሽን የተንተራሰ ሲሆን “እሰይ እሰይ! እልል በይ ጉሜ!” ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ በማንኛውም የለውጥ ንፋስ ውስጥ ጊዜን፣ ወዳጅንና ባላንጣን ማሰብ ዓይነተኛ ብልህነት ነው፡፡ ጊዜው እንጂ ሁኔታው አይደለም ጥፋተኛው፡፡ “ሳህን ቢጠፋ አብረን በላን” እንደሚባለው የትግሪኛ ተረት፤ “የሰሜን ብርድ ከማትወድደው ጋር ያስተቃቅፋል” የሚለው ተረት ዋና ጉዳይ ነው!

Published in ርዕሰ አንቀፅ
  • የመን እንደ ሶማሊያ መታመሷ፣ ለኤርትራ መንግስት አመቺ ይሆናል

የኤርትራ መንግስት አካባቢውን እየበጠበጠ ስለሆነ በጋራ እንመክተዋለን ያሉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጅቡቲ ፕሬዚዳንት፤ በኤርትራ መንግስት ላይ የተጣለው አለማቀፍ ማዕቀብ እንዲቀጥል
የጠየቁ ሲሆን፤ የኤርትራው ፕሬዚደንት በበኩላቸው ውንጀላውን አስተባበሉ፡፡ሰሞኑን  በጅቡቲ የሶስት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ፤ የኤርትራ መንግስት ለአካባቢው አገራት ፀጥታ ስጋት ስለሆነ ኢትዮጵያና ጅቡቲ በጋራ እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡ የኤርትራ መንግስት የጅቡቲን ጨምሮ የአካባቢውን አገራት ፀጥታ እያወከ ነው ያሉት ፕሬዚደንት ኦማር ጊሌ፤ ኤርትራ ላይ የየተጣለው ማዕቀብ እንዲቀጥል ከጠ/ሚ ኃይለማርያም ጋር መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ድንበራቸውን በጋራ ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ጠ/ሚ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ የኤርትራ መንግስት አካባቢውን ከመበጥበጥ ስላልተቆጠበ ስድስት አመት ያስቆጠረው አለማቀፍ ማዕቀብ እንዲቀጥልና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድበት ንጠይቃለን ብለዋል፡፡ በአፍሪካ ህብረት፣ ከዚያም በተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክር ቤት አማካኝነት ኤርትራ ላይ ማዕቀብ የተጣለው፣ የሶማሊያ አሸባሪዎችን በመደገፍና በማስታጠቅ አካባቢውን ይበጠብጣል በሚል ምክንያት እንደሆነ ይታወሳል፡፡ የኤርትራ መንግስት የሶማሊያ አሸባሪዎችን እንዲሁም በየአገሩ አማፂ ቡድኖችን ያስታጥቃል በሚል ከፍተኛ ስጋት ያደረባቸው አገራት በተለይም ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከየመን ጋር ትብብር በመፍጠር ጫና ለማሳደር ሲጥሩ የነበረ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የየመን ቀውስ እየተባባሰ መንግስት አልባ መሆኗ ለሁለቱ አገራት ይበልጥ አሳሳቢ ሆኖባቸዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ የሚሰነዘረውን ውንጀላ በማስተባበል፤ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እየላላ ስለመጣና ማዕቀቡ ይነሳል የሚል ስጋት ስላደረባቸው ነው ውንጀላውን የሚደጋግሙት ብለዋል፡፡ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባሰራጨው ተመሳሳይ ምላሽ፣ ኢትዮጵያ የድንበር ዳኝነትን
ባለማክበር አካባቢውን ትበጠብጣለች በማለት የወነጀለ ሲሆን፤ ከጅቡቲ ጋር በኳታር ሸምጋይነት ድርድር ከተጀመረ በኋላ የጅቡቲ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ማበሩ አሳዝኖናል ብሏል፡፡ የኤርትራ መንግስት የሶማሊያ አሸባሪዎችን በማስታጠቅ፣ የጎረቤት አገራትን ፀጥታ ያውካል  በሚል በቀረበ ክስ፣ በ2001 የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ላይ ማዕቀብ ሲጥል፤ ከቻይና እና ከራሺያ የተአቅቦ ድምፅ በስተቀር የምክር ቤቱን ይሁንታ በማግኘት ያለፈ ውሳኔ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሰነዶችን በማስረጃነት ያቀረበች ሲሆን የኤርትራ መንግስት ጐረቤት አገራትን የሚበጠብጠው በመከላከያ ሚኒስትሩ ጀነራል ኤፍሬም ስብሀት አስተባባሪነት እንደሆነና፤ የአየር ሀይል እና የባህር ሀይል አዛዞችን ጨምሮ 12 ጀነራሎች የእንቅስቃሴው መሪዎች እንደሆኑ በሰነዶቹ ተዘርዝሯል፡፡ የኤርትራ የባህር ሀይል ዋና አዛዥ ሜ/ጀ ሁመድ ካሪካሬ፣  ባለፈው አመት የሞቱት  ሜ/ጀ ገብረ እግዚአብሄር አንደማርያም፣ ሜ/ጀ ሀይለ ሳሙኤል፣ የኤርትራ ብሄራዊ ደህንነት አዛዥ ብ/ጄ አብርሀ ካሳ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲን ፀረ ሰላም ሀይሎች በማስተባበር ያሰማራሉ ተብለው በስም ተጠቅሰው ነበር፡፡

Published in ዜና

“መንግስት ልጄን የመጠየቅ መብቴን ያስከብርልኝ”

      በ“ፍትህ” ጋዜጣ ላይ በዋና አዘጋጅነት ሲሰራ በጻፋቸው ፅሁፎች ክስ ተመስርቶበት የ3 ዓመት እስራት የተፈረደበት የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወላጅ እናት፣ ልጃቸውን የመጠየቅ መብታቸው እንዲከበርላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤትና ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት አቤቱታቸውን በደብዳቤ አቀረቡ፡፡ በዝዋይ ማረሚያ ቤት እንደሚገኝ የተጠቆሙትን ልጃቸውን ከአንድ ወር በላይ ማየትም ሆነ ጊዜ መጠየቅ እንዲሁም ስንቅ ማቀበል እንዳልቻሉ የጠቀሱት የጋዜጠኛው ወላጅ እናት ወ/ሮ ፋናዬ፤ የተመስገን ታናሽ ወንድም ታሪኩ፣ ከአንድ ወር በፊት ስንቅ ሊያደርስለት ሄዶ ተደብድቦ መመለሱን፣ ከዚያን ጊዜ በኋላም ቤተሰቦች ተመስገንን ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ “ልጄ በህይወት ይኑር አይኑር ማወቅ አልቻልኩም” ያሉት ወ/ሮ ፋናዬ፤ “እኔ ልጄ ይፈታ አይደለም ያልኩት፤ እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቹ እንዲጠይቁትና ስንቅ እንድናቀብለው እንዲሁም ህክምና እንዲያገኝ ይፈቀድልን ነው ያልኩት” ብለዋል፡፡ ተመስገን ሁለተኛ ልጃቸው መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ ፋናዬ፤ “ስታመም የሚያስታምመኝ፣ ከጎኔ ሆኖ ድጋፍ የሚያደርግልኝን ልጄን ያለበትን ሁኔታ አለማወቄና ስንቅ ማቀበል አለመቻሌ አሳዝኖኛል” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ አክለውም፤ “መንግስት ልጄን የመጠየቅና ስንቅ የማቀበል መብቴን እንዲያስከብርልኝ ማጸናለሁ” ብለዋል፡፡ የተመስገን ታናሽ ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ በበኩሉ፤ ከ40 ቀናት በፊት ስንቅ ለማድረስና ለመጠየቅ ሄዶ በጥበቃዎች መጠየቅ አትችልም ተብሎ ሊመለስ ሲል፣ ማንነቱ ተጠይቆ የተመስገን ወንድም መሆኑን ሲገልፅ፣ ድብደባ ተፈፅሞበት ወንድሙን ሳያገኘው መመለሱን ተናግሯል፡፡  
የሬዲዮ መገናኛ የያዘ ፖሊስ “ወንድሙ ነህ?” ብሎ እንደጠየቀው፣ “አዎ!” ሲለው በጥፊ እንደመታውና ሌሎችም ተረባርበው በርካታ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ ድብደባ እንደፈፀሙበት፣ የያዘው ምግብም እንደተደፋ ታሪኩ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ የተመስገን ወላጅ እናት የተማፅኖ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለእንባ ጠባቂና ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሰኞ መግባቱን የጠቆመው ታሪኩ፤ የመንግስትን ቀና ምላሽ እየተጠባበቅን ነው ብሏል፡፡ የቀድሞ የ“ፍትህ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የ“ፋክት” መፅሄት አምደኛ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ፤ በ“ፍትህ ጋዜጣ ላይ ሲሠራ በተለያዩ ህትመቶች በፃፋቸው ጽሑፎች፣ ወጣቶችን ለአመፅ በማነሣሣት እና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃሰት በመወንጀል ክስ ተመስርቶበት ጥቅምት 17 ቀን 2007 ዓ.ም ፍ/ቤት  የ3 አመት ፅኑ እስራት እንደበየነበት ይታወሳል፡፡ በጉዳዩ ላይ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡

Published in ዜና

አምና ከጫት  ኤክስፖርት ከ5 ቢ. ብር በላይ ተገኝቷል

    በጫትና ሺሻ አመራረት፣ ንግድና አጠቃቀም ላይ የሚያተኩር አዲስ ህግ ሊወጣ ሲሆን ፍትህ ሚኒስቴር ጫትና ሺሻን አስመልክቶ ያዘጋጀውን ረቂቅ ህግ የዓለም ጤና ድርጅትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንዲወያዩበት ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጿ፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ ሰሞኑን በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ጫት በዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችልና በጫትና ሺሻ አመራረት፣ ንግድና አጠቃቀም ላይ ገደቦችን የሚጥል አዲስ ረቂቅ ህግ ወጥቷል፡፡ በፍትህ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ይኸው ረቂቅ ህግ፤ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚካሄደው አገር አቀፍ ሲምፖዚየም ላይ ለውይይት ቀርቦ ማስተካከያዎች ከተደረጉበት በኋላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ በቅርቡ ይካሄዳል በተባለው አገር አቀፍ የጫት ሲምፖዚየም ላይ ታላላቅ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚገኙና ጫት በዜጐች ላይ እያስከተለ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አስመልክቶ በምሁራን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚቀርቡ ዶ/ር ከሰተብርሃን ጨምረው ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአውሮፓና አሜሪካ ያላት የጫት ሽያጭ በእጅጉ በመቀዛቀዙ ምርቶቿን በአብዛኛው የምትልከው ለየመን፣ ሶማሊያና አረብ አገራት ሲሆን ባለፈው ዓመት ጫት ከአገሪቱ የኤክስፖርት ምርቶች በአራተኛነት ደረጃ ላይ ሆኖ፣ 270 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቶበታል፡፡  


Published in ዜና

ሩስያ ለግብጽ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ልትገነባ ነው

     የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሹክሪ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያው አቻቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ትላንትና በአዲስ አበባ የሁለትዮሽ ውይይት አደረጉ፡፡ በውይይቱ ላይ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር እንደተገኙም ታውቋል፡፡ ሁለቱ ሚንስትሮች በአገራቱ መካከል የተጀመሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት ውይይቶችን እንደሚቀጥሉ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ባድር አብደል አቲ ገልጸዋል፡፡በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ፤ በሰሜናዊ ሲና አካባቢ ታጣቂዎች ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ውይይት ሰርዘው ወደአገራቸው መመለሳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያው አቻቸው ያደረጉላቸውን ግብዣ በመቀበል ውይይቱን ለመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቁሟል፡፡በሌላ በኩል ሩስያ፤ ለግብጽ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ልትገነባ እንደሆነ የሁለቱ አገራት መሪዎች ባለፈው ማክሰኞ በካይሮ በሰጡት የጋራ መግለጫ እንዳስታወቁ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ከግብጹ አቻቸው አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋር የሃይል ማመንጫ
ግንባታ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ስምምነቱ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሚደረስበት ከሆነ፣ ጉዳዩ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በግብጽ አዲስ የአቶሚክ ኢንዱስትሪ ጅማሬ ይሆናል ብለዋል፡፡ግብጽ ከዚህ በፊት ባቋቋመችውና ከአሌክሳንድሪያ የወደብ ከተማ ምዕራባዊ የሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ ላይ በምትገኘው ዳባ ከተማ ውስጥ ባለው የኒውክሌር ምርምር ጣቢያ ላይ የሚገነባው ይህ የሃይል ማመንጫ፣ እያንዳንዳቸው 1ሺህ 200 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው አራት ማብላያዎች እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡ግንባታው በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት እየተስፋፋ ላለባት ግብጽ ሁነኛ መፍትሄ ይሆናል ተብሏል፡፡ የግብጹ አሽራቅ አል አውሳት ድረገጽ በበኩሉ፤ ምንም እንኳን የአገራቱ መሪዎች በይፋ ባያረጋግጡትም፣ አገራቱ ከሃይል ማመንጫ ግንባታው በተጨማሪ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት ፈጽመዋል ሲል ኢንትራ ፋክስ የዜና ተቋምን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

Published in ዜና

በ6 ወራት ውስጥ ከተገመተው እጥፍ የመንገድ ጉዳት ደርሷል
የመንገድ ትራፊክ ፍሰቱን ለመቆጣጠርና መንገዶች ለተሽከርካሪዎችና ለእግረኞች አመቺ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቦ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የተተከሉ የትራፊክ ደህንነት መቆጣጠሪያ ምልክቶች በህገወጦች እየተሰረቁ መሆኑ ተገለፀ፡፡ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መብት ጥበቃና አስተዳደር ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ አቶ አስመላሽ ኪዳነማርያም ትናንት በጽ/ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ለተለያዩ የትራፊክ ደህንነት አገልግሎት ታስበው የተተከሉ ምልክቶች በህገወጦች ከቦታቸው እየነሱና እየተሰረቁ ነው፡፡ በቀንና በምሽት ይካሄዳል በተባለው የመንገድ ምልክቶች ዝርፊያ ላይ ተሣታፊ የሚሆኑት ህገወጦች፣ ህጋዊ መስለው ከሚመለከተው አካል የተላኩ በማስመሰል፣ መስለው ድርጊቱን እንደሚፈፅሙ ጠቁመው በታክሲ አሽከርካሪዎችና በሌሎች ህገወጦች ጭምር ድርጊቱ እየተፈፀመ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ተክለሃይማኖት፣ በርበሬ ተራ አካባቢና ሣሪስ ህገወጥ የትራፊክ ምልክቶች ዝርፊያ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚጠቀሱ እንደሆኑም አቶ አስመላሽ ገልፀዋል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ
በመንገድ ሀብት ጥበቃና አስተዳደር ላይ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክተው ሃላፊው በሰጡት መግለጫ፤  በስድስት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ 600 ህገወጦች ጉዳት ያደርሳሉ ተብሎ የተገመተ ቢሆንም በተጠቀሱት ጊዜያት በመንገዱ ላይ የደረሰው ጉዳት 1157 ገደማ እንደሆነና ይህም የግምቱን 192% እንደሚሸፍን ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

የፓርኪንግ አገልግሎት ለግል ኩባንያ ተሰጥቷል
የአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የአውሮፕላን ማረፊያና ተርሚናል ግንባታና የመንገደኞች ማስተናገጃ፣ የደህንነትና የመኪና ማቆሚያ ማስፋፊያ ስራ እየተሰራ ሲሆን ፕሮጀክቱ በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን አስመልክቶ ትናንት የኢትዮጵያ ኤርፖርት ድርጅት የስራ ኃላፊዎች ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫና የመስክ ጉብኝት ላይ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ደንበኞች የማስተናገድ ዓመታዊ አቅሙ ከ7 ሚሊዮን ወደ 22 ሚሊዮን እንደሚደርስ ተጠቁሟል፡፡ መንገደኞችን ለማስተናገድ የሚያገለግሉ አሁን ካለው አለማቀፍ ተርሚናል ግራና ቀኝ አለማቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ተርሚናሎች የሚገነቡ ሲሆን ተርሚናሎቹ የቪአይፒ እና ገንዘብ  ከፍለው ደረጃቸውን ጠብቀው ለሚጓዙ (የ ሲአይፒ)ደንበኞች ማስተናገጃ ቦታዎች እንደሚኖሩ ተገልጿ፡፡
ሻንጣዎችን የመፈተሽ አገልግሎት፣ መሳሪያዎች ተከላና ሲስተም ዝርጋታ ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የእንግሊዝ ኩባንያ እያከናወነ ሲሆን አሁን ያለውን በሰዓት 1500 ሻንጣ የመፈተሽ አቅም ወደ 3300 ያሳድገዋል ተብሏል፡፡ ሻንጣዎች በበረራ ቁጥራቸው በመለየት  ከዚህ ቀደም የነበረውን የመደበላለቅና ሻንጣዎች ወደ አልተፈለገ ቦታ የመጫን ችግርን የሚዘረጋው የፍተሻ እንደሚያስቀር ተገልጿል፡፡ አገልግሎቱ ከሁለት ወር በኋላ እንደሚጀመርም ተጠቁሟል፡፡ የኤርፖርቱን ደህንነት ለመጠበቅ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የግለሰብን ማንነት በጥራት የሚያሳዩ እንዲሁም በጨለማ  ምስሎችን ለይተው የሚያቀርቡ ዘመናዊ ካሜራዎች የሚገጠሙ መሆኑን የኤርፖርቱ የስራ አመራሮች ገልፀዋል፡፡ በኤርፖርቱ ግቢ ውስጥ የመኪና ፓርኪንግ አገልግሎት ዩ-ስትሬት ፓርኪንግ ለተሰኘ መቀመጫውን አሜሪካን ላደረገ የኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ኩባንያ እንደተሰጠ የተጠቆመ ሲሆን የፓርኪንግ ቦታ ግንባታው ከኤርፖርቱ ማስፋፊያ ጋር ተያይዞ ባለሶስት ፎቅ ፓርኪንግ እንደሚገነባም ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት ይጀምራል የተባለው ፓርኪንጉ በማሽን የታገዘ ዘመናዊ የክፍያ ስርአትን የሚከተል ሲሆን ከሚገኘው ገቢ ላይ 70 በመቶ ኤርፖርቶች ድርጅት 30 በመቶ ኩባንያው ይከፋፈላሉ ተብሏል፡፡ ለፓርኪንጉ አገልግሎት የሚውሉ እቃዎች ግዢ በ2.8 ሚሊዮን ብር መፈፀሙም ተጠቁሟል፡፡ በአጠቃላይ በሶስት ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው የኤርፖርቱ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በ80 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ይከናወናል ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ውስጥ ይገነባል ለተባለው ግዙፍ አለማቀፍ ኤርፖርት ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ 5 ቦታዎች ተመርጠው የመንግስት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡
ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ሊፈጅ እንደሚችል የተገመተው ኤርፖርቱ የራሱ ብቻ የሆነ የፍጥነት መንገድና የሃይል አቅርቦት ይኖረዋል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን የት አካባቢ እንደሚገነባ ከሁለት ወር በኋላ ይታወቃል ተብሏል፡፡  

Published in ዜና

         በኬንያ አየር መንገድ የገንዘብ ድጋፍ በናይሮቢ ኬንያ ለሚደረገው የጐልፍ ሳፋሪ የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ማጣሪያ ያለፉ ታወቁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ 75 የኬንያ ኤርዌይስ የጐልፍ ሳፋሪ አባላት፣ ለአሸናፊዎች አሸናፊ ማጣሪያ ባደረጉት ውድድር ከወንዶች ሰለሞን ታደሰ እና ኮሎኔል ማይክ ቺፓይሌ፣ ከሴቶች ደግሞ ዶ/ር ሃ ኦክሱን አልፈዋል፡፡ የውድድሩ ዓላማ ኬንያ ኤርዌይስ በሚበርባቸው አገሮች ያሉ ደንበኞቹን ለማወቅ፣ አዳዲስ ደንበኞችን ለመተዋወቅና እንዴት አብረው መቀጠል እንደሚችሉ ለመነጋገር በየሁለት ዓመቱ የሚዘጋጅ የጐልፍ ሳፋሪ እንደሆነ የጠቀሱት የአየር መንገዱ የስፖንሰርና ኢቨንት ማናጀር ዊኒ ኦናች፤ የዕለቱ ውድድር፣ በእንግሊዝ ቅኝ ስር ይተባበሩ የነበሩ 10 የአፍሪካና የኤስያ የጋራ ብልጽግና (ኮመንዌልዝ) አገራት ማርች 28 ቀን 2015 በናይሮቢ ለሚደረገው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድድር ማጣሪያ እንደሆነ ይገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የጎልፍ ጫወታ ስላልተለመደ አባሎቻቸው 75 ቢሆኑም፣ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበሩ አፍሪካና እስያ አገሮች 8ሺ አባላት እንዳሏቸው የጠቀሱት ማነጀሯ፤ በአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ለመሳተፍ ወደ ናይሮቢ የሚጓዙ ተወዳዳሪዎች አጠቃላይ ወጪ (የአውሮፕላን፣ የሆቴል…) ተችሏቸው ለ7 ቀናት እዚያው እንደሚቆዩ ተናግረዋል፡፡   በአዲስ አበባው የጐልፍ ውድድር የ19 እና የ20 ዓመት ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡ አቤሮን ቡሾ የ19 ዓመት ወጣት ሲሆን 12ኛ ክፍል አጠናቋል፡፡ አቤሮን የ2 ሃንድ ካፕ (ደረጃ) ጐልፍ ተጫዋች ነው፡፡  ጀማሪ ጐልፍ ተጫዋች 28 ሃንድ ካፕ ሲሰጠው ፕሮፌሽናል የጎልፍ ተጫዋች ደግሞ ዜሮ ይሰጠዋል፡፡ አቤሮን ፕሮፌሽናል የጐልፍ ተጫዋች ለመሆን 2 ሃንድ ካፕ ቀርቶታል ማለት ነው፡፡ አቤሮን ጐበዝ የጐልፍ ተጫዋች ስለሆነ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቶ በቅርቡ ወደ ፍሎሪዳ እንደሚጓዝ የአዲስ አበባ ጐልፍ ክበብ ም/ኃላፊ ነግረውኛል፡፡ “ፍሎሪዳ፣ ዓለምአቀፍ ማናጅመንት ኦፍ ጐልፍ አካዳሚ (IMG) ስላለ እዚያ እየተጫወትኩ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን እንድቀጥል ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቻለሁ” ብሏል አቤሮን፡፡ “ማን ያውቃል… አንድ ቀን እንደ ማይክል ዉድ ታዋቂ የሆነ ኢትዮጵያዊ የጐልፍ ተጫዋች እናይ ይሆናል” በማለት ም/ኃላፊው የአቤሮን ችሎታ ገልፀዋል፡፡ ናታኒም ፋንታሁን የ20 ዓመት ወጣትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው፡፡ ናታኒም ጐልፍ መጫወት የጀመረው በ15 ዓመቱ ሲሆን አሁን ደረጃው 3 ሃንድ ካፕ ነው፡፡ ስለጐልፍ ጨዋታ ማንም እንዳላሳየው የተናገረው ናታኒም፣ እያየ መማሩን ነው ተናግሯል፡፡ ጨዋታ ሲጀምር እንደጀማሪ የተሰጠው 28 ሃንድ ካፕ ሳይሆን 22 እንደነበር የተጠቀሰው ናታኒም፤ ወደፊት በትምህርቱ ላይ ችግር ካልፈጠረበት በጐልፍ ጨዋታ ለመቀጠል ሐሳብ እንዳለው ገልጿል፡፡

Published in ዜና

            በሽብርተኝነት የተከሰሱትን የዞን 9 ጦማሪያንና ጋዜጠኞችን አስመልክቶ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ለተባበሩት መንግስታት አቤቱታ አቀረቡ፡አቤቱታውን ያቀረቡት መቀመጫቸውን ኬንያ - ናይሮቢ ያደረጉት “የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት” እና “ፍሪደም ናው” የተባሉት የሰብአዊ መብት ተቋማት እንደሆኑ ታውቋል፡፡ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ቡድን የቀረበው አቤቱታ፤ ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ አላግባብ መታሰራቸውን፣ እስሩ አለማቀፍ መብቶችንም ሆነ የወንጀል ህግ መሰረቶችን የጣሰ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ በእስራቸው ወቅት እየደረሰባቸው ነው የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በዝርዝር ያካተተ እንደሆነ በድርጅቶቹ ድረገፅ ላይ ከሰፈረው ባለ 23 ገፅ አቤቱታ ሰነድ ለማወቅ ተችሏል፡፡ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ከታሰሩ ጊዜ ጀምሮ ለ19 ጊዜያት ያህል ፍ/ቤት መቅረባቸውን የጠቀሰው አቤቱታው፤ ተገቢውን ፍትህ ሳያገኙ በህግ የተሰጣቸው ሰብአዊ መብት እየተጣሰ ነው ብሏል፡፡ ከወራት በፊት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች ቡድን፤ የኢትዮጵያ መንግስት የጸረ - ሽብርተኝነት ህጉን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለማፈኛነት እንዳይጠቀም ጠይቆ ነበር፡፡ “ሽብርተኝነትን መዋጋት በአሁን ወቅት አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን በሚጥስ መልኩ መሆን የለበትም” ማለቱ ይታወሳል፡፡
በእነ ሶሊያና ሽመልስ መዝገብ በሽብር ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት 6 ጦማሪያን እና 3 ጋዜጠኞች፤ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ፍ/ቤት ቀርበው ሰብሳቢ ዳኛው እንዲነሱላቸው መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን ፍ/ቤቱም በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠትና በክሱ የተጠቀሱትን ድርጊቶች ፈፅመዋል አልፈፀሙም በሚለው ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም
ቀጠሮ መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

Published in ዜና
Page 8 of 13