ኮሪያ እስከ ሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ የጃፓን ቅኝ ግዛት ነበረች፡፡ የሁለተኛው የአለም ጦርነት በጃፓን ሽንፈት ተጠናቀቀ፡፡ ሽንፈቷን ተከትሎ የጃፓን አገዛዝ በኮሪያ ላይ አበቃ፡፡ አሜሪካን ቻይና እና ታላቋ ብሪታኒያ የካይሮ ስምምነት በመባል የሚታወቀውን ሰነድ አፀደቁ፡፡ የኮሪያ ሰሜኑ ክፍል በሶቪየት ህብረት፤ ደቡብ ክፍል ደግሞ በአሜሪካን የሞግዚት አስተዳደር ስር እንዲቆይ የሚያደርገው ስምምነት ተግባራዊ ሆነ፡፡ ይህ ክፍፍል ዘላቂ ይሆናል ተብሎ የታሰበ ባይሆንም፣ የሁለተኛውን የአለም ጦርነት ማብቃት ተከትሎ አሸናፊዎቹ ሀይሎች የቀዝቃዛው ጦርነት ሰለባ የማድረግ ብቃት ስለነበራቸው የተከናወነ ነበር፡፡ የቀዝ
ቃዛው ጦርነት ሁለት ተቃራኒ ጎራዎች ቀደም ብለው የኮሪያን ሰሜንና ደቡብ በመከፋፋላቸው፣ ኮሪያውያን የቀዝቃዛው ጦርነት ማሟሟቂያ ሆኑ። በ1950 ሰሜን ኮሪያ በቻይናው ማኦ ዜዱንግ እና በስታሊን አለሁ ባይነት ደቡብ ኮሪያን ወረረች። ከሶስት አመት በኋላ በተደረሰ ስምምነት ጦርነቱ አብቅቶ፣ ሰሜን እና ደቡብ  ኮሪያ የሚለው  ክፍፍል ቋሚ ሆኖ ፀና፡፡ የስምምነቱ አካል በሆነው እና የኮሪያን ጉዳይ ለማየት በሚል የተጠራው የጄኔቫ ኮንፈረንስም ምንም እንኳን ከብዙ አገሮች የአንድነት አንጀንዳ ብልጫ እንዲያገኝ ቢሞከርም የኮሪያውያኑን አንድ ማድረግ ሳይችል ተበተነ፡፡
እጣፈንታቸው በሌሎች እንዲወሰን ግድ የሆነባቸው ኮሪያዎች፤ ደቡብ እና ሰሜን ተብለው ሲለያዩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ዝምድና ከድንበር ጋር አብሮ እንዲቆራረጥ ሆነ፡፡ ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ የሚገኙ የአንድ ቤተሰብ አባላትን የነጠለው ውሳኔ፣ ከሀያ ሁለት አመታት በኋላ ይፋ በተደረገ ሚስጥር መፍትሄ ያገኘ መሰለ፡፡ የሁለቱ አገሮች መሪዎች በድብቅ አንዱ የአንዱን ዋና ከተማ እንደጎበኙ እና ዋና የጉብኝቱ አላማም የሁለቱ ኮሪያዎች ሰላማዊ ውህደትን በመሻት የተከናወነ መሆኑን የሁለቱ ሀገር መሪዎች ገለፁ፡፡ የሰሜንና የደቡብ ኮሪያ የጋራ ስምምነት የተባለ ሰነድ መፈራረማቸውን አወጁ። ይሁን እንጂ፤ ይህን ያስፈፅማሉ በሚል ከሁለቱ አገሮች በተውጣጡ ልዑካን የተቋቋመው ኮሚቴ ያለምንም ውጤት ከአንድ አመት በኋላ ታገደ፡፡ በ1990 የሁለቱ ኮሪያዎች ጠቅላይ ሚኒስትሮች  ሲኦል ላይ ተገናኝተው የኮሪያውያንን አንድነት በተመለከተ ውሳኔዎችን ቢያስተላልፉም፣ ከኒኩሊየር ማበልፀጊያ ፖለቲካ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ውዝግብ በመፍጠሩ ውጤት አልባ ሆነ፡፡ ከአመት በኋላ፤ እንደገና የሰሜን እና የደቡብ ኮሪያ የጋራ ስምምነትን የሚገልፅ ሰነድ አወጡ፡፡  የሰነዱ ዋነኛ አላማም፤ የሁለቱን ኮሪያዎች ሰላማዊ ውህደት የሚመለከት እንደሆነ አወጁ፡፡
የዚህ ውህደት እርምጃ በ2000 ተጀምሮ በ2007 በሰሜን ኮሪያ መንግስት ውሳኔ እንዲቆም የተደረገው ከሀምሳ አመታት በላይ የተለያዩ ቤተሰቦችን የማገናኘቱ ስራ ሰሞኑን እንደገና አገርሽቶ የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት ሆኗል፡፡ ቤተሰቦችን ማገናኘቱ በሚቀጥለው ወር እንደሚጀመር ከስምምነት ላይ ተደርሶ የነበረ ቢሆንም ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካን ጋር በምታደርገው የፖለቲካ ወንድማማችነት ምክንያት ውሳኔዬን ልሰርዝ እችላለሁ ስትል ሰሜን ኮሪያ አስጠንቅቃለች፡፡
በተለያዩ የፖለቲካ ወገንተኞች ፍላጎት እና ውሳኔ፤ እንዲሁም ፅንፈኛ አቋም በያዙ መሪዎቻቸው እሰጥአገባ ሳቢያ የተነጣጠለ የቤተሰብ አባላትን የማገናኘቱ ፕሮግራም ለኮርያዊያኖች ከጥልቅ ስሜታቸው ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው፡፡ ቀን በሄደ እና እድሜ በገፋ ቁጥር በሞት መለየት ሊመጣ እንደሚችል ሲያስቡት ጉጉታቸው የበለጠ ይበረታል፡፡
የደቡብ ኮሪያ የቀይመስቀል ማህበር ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በ1988 ከቤተሰባቸው ጋር ለመቀላቀል ማመልከቻ ካስገቡ 127፣400 በሰሜን ኮሪያ የሚኖሩ ዜጐች ውስጥ አርባ ሺህ ያህሉ ቤተሰቦቻቸውን መቀላቀል ሳይችሉ ህይወታቸው ማለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እስከ አሁን 16ሺ 200 ኮሪያውያን በአካል፣ 3ሺ 740 የሚሆኑት ደግሞ በቪዲዮ ከቤተሰባቸው ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ቤተሰቦችን የማገናኘቱ ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት ባሉት ቀደምት አመታት፣ ኮሪያውያኑ በያሉበት ከቤተሰቦቻቸው ጋር የፖስታ የስልክም ሆነ የኢሜይል መልእክት መለዋወጥ የማይችሉ ሲሆን ያለ መንግስት ፈቃድም ድንበር ማቋረጥ ተከልክለው ቆይተዋል፡፡
የ“ሁለቱ ኮሪያዎች ውህደት” የሚለው መፈክር ለዘለቄታው ተግባራዊ አይሆንም የሚሉ ወገኖች አሉ። ለዚህ ሀሳባቸው በመከራከሪያነት የሚያቀርቧቸውን ማሳመኛዎች አንድ ሁለት ብለው ይዘረዝራሉ፡፡ አንደኛ፤ ሁለቱ ኮሪያዎች በመለያየት ባሳለፏቸው አመታት ውስጥ ብዙ የተለያዩ ማንነቶችን አብቅለዋልና ይህ ልዩነት መቼም ወደ መታረቅ ሊመጣ አይችልም፤ ይላሉ፡፡
ሁለተኛ፤ ተለያይተውም በቆዩበት ብዙ አስርት አመታት የነበራቸው ግንኙነት እጅግ የሻከረ መሆኑ ለውህደት ባይሆንም … ቢያንስ በሁለቱ መሀል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ሊያግዝ ይችል ይሆናል። ሶስተኛው፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀል የሚፈልጉት ኮሪያውያን እድሜ ሰባ እና ከዛ በላይ በመሆኑ፤ ኮሪያን አንድ በነበረች ጊዜ የሚያውቃት ትውልድ እየከሰመ በአዲስ ትውልድ በመተካቱ ምክንያት ነው፤ ብለው ማሳመኛዎቻቸውን ይተነትናሉ፡፡ የውህደት ጥያቄውም ልክ እንደ ትውልዱ እየከሰመ ይሄዳል፤ ውህደቱ ለቀድሞው ትውልድ እንጂ ለአዲሱ ትውልድ ትርጉም የሚሰጥ ሊሆን አይችልም ይላሉ፡፡
በቀዝቃዛው ጦርነት ምክንያት ሁለት አገር የሆኑት ኮሪያውያን፤ ሰሞኑን ደግሞ ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካን ጋር ወግናለች በሚል ምክንያት ከሀምሳ አመታት በላይ ከተለዩዋቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር የመገናኘት ህልማቸው ጥያቄ ላይ ወድቋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

       ወጣት ይስሃቅ ካሣሁን ይባላል፡፡ ፒያኖ የመጫወት ፍላጐት ያደረበት ገና የ15 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር፡፡ ጊዜው 2002 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ በገርጂ የኮርያ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሚገኘው የ “ጉድ ኒውስ ቸርች” አዳራሽ ፒያኖ የሚማሩ ልጆችን ሲመለከት ነው ፍላጐቱ የተቀሰቀሰበት፡፡ እሱም እንደነዚያ ልጆች ፒያኖ የመማር ዕድል ቢያገኝ ተመኘ፡፡ ግን እድል አልቀናውም፡፡ ስለዚህም በምሳ ሰዓት ሰው ጭር ሲል ወደ አዳራሹ ተደብቆ እየገባ፣ በፈቃዱ የፒያኖውን ቁልፎች መነካካት ጀመረ፡፡ የቤተክርስቲያኑ የጥበቃ ሠራተኞች ግን አላስደርስ እያሉ መከራውን አበሉት፡፡ በተደጋጋሚ አግኝተው እንዳባረሩትም ይስሃቅ ያስታውሳል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ አዳራሹን ይቆልፉበት ነበር፡፡ ክልከላው ቢያይልበትም ተስፋ አልቆረጠም፡፡ የአዳራሹ በር ሲቆለፍበት  በመስኮት ሁሉ እየገባ ፒያኖ ይለማመድ እንደነበር ይናገራል፡፡
አንድ ዓመት ያህል እንዲህ ካሳለፈ በኋላ የታዳጊውን የፒያኖ ፍቅር ያስተዋሉት የቤ/ክርስቲያኑ ኃላፊ፤ ሌላ አዳራሽ ውስጥ ባለ ፒያኖ እንዲለማመድ ፈቀዱለት፡፡ ይሄኔ ይስሃቅ በደስታ ጮቤ ረገጠ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ስራዬ ብሎ ፒያኖ ማጥናት የጀመረው፡፡ “በቀን ለ10 ሰዓታት ቁጭ ብዬ ፒያኖ እለማመድ ነበር” ይላል ወጣቱ የፒያኖ ተጫዋች። መጀመሪያ ላይ ከኢንተርኔት ሙዚቃዎችን እየገለበጠ ነበር የሚለማመደው፡፡ ታዋቂና ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን ለማወቅና ለማጥናትም ብዙ እንደጣረ ይናገራል፡፡ ከዚያም ትኩረቱን ወደ አገርኛ የፒያኖ ሙዚቃዎች በማድረግ በተለይ የእማሆይ ፅጌ ማርያም ዜማዎችን ይሞካክር ጀመር፡፡ አሁንም ድረስ በእማሆይ ሥራዎች እንደሚመሰጥ ገልጿል፡፡
ቤተክርስትያኑ ውስጥ የዕውቅ ሙዚቀኞችን ስራዎች ሲጫወት ያዳመጡ ሰዎች “ለምን የራስህን ሙዚቃ አትሰራም?” እያሉ ሲገፋፉት ሞራልና መነቃቃት እንዳገኘ የሚናገረው ይስሃቅ፤ በ2003 ዓ.ም “Hope and Reload” የተሰኘውን የመጀመርያ ሙዚቃውን እንዳቀናበረ ይገልጻል። በእርግጥ ሙዚቃውን ለመድረስ ከፈጀበት ጊዜ ይልቅ ሥራውን በቪድዮ ለመቅረፅ የበለጠ ጊዜ እንደወሰደበት አልሸሸገም፡፡ የ11 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውን “Hope and Reload” ለመቅረፅ 3 ወር ፈጅቶበታል፡፡ ቀረፃው እንደተጠናቀቀም በዩቲውብ ድረገጽ ላይ ለተመልካቾች ዕይታ አበቃው፡፡
በዩቲውብ የተለቀቀው አዲስ ስራው ያልጠበቀው ምላሽ ያስገኘለት ሲሆን “ሊንክ” ተደርጐ ከ20 በላይ ድረገፆች ላይ ሊሰራጭለት እንደቻለ ይናገራል፡፡ ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ፈፅሞ ያልገመታቸው ዝነኛ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሥራውን አድምጠው የማበረታቻ አስተያየት ሰጥተውታል፡፡ በያኒ የሙዚቃ ቪድዮ ላይ የትንፋሽ መሳሪያ የሚጫወተውና በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሙዚቃ መምህር የሆነው ኪላኒ ተጠቃሽ ነው፡፡ የይስሃቅን ሙዚቃ አስመልክቶ በኦፊሴላዊ ድረገፁ ባሰፈረው አስተያየት “ድንቅ የሙዚቃ ሥራህን ስላሰማኸን አመሰግንሃለሁ፡፡ ለማደግና ሥራህን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ በምታደርገው ጥረት ሁሉ መልካሙን እመኝልሃለሁ” በማለት አድንቆታል። ሌላው ዝነኛ አሜሪካዊ ሙዚቀኛና የትሩግሩቭ ሪከርድስ ባለቤት ቶማስ ዶንከር በበኩሉ፤“እንዲያ ነው እንጂ! በጣም ውብ ሥራ ነው፡፡ ዋው! በጣም ተደምሜበታለሁ” ሲል አወድሶታል፡፡ ከማይክል ቦልተንና ከአሜሪካዊው ራፐር አይስኪውብ ጋር የሚሰራው ሳክስፎኒስቱ ስኮት ማዮ በሰጠው አስተያየት፤“ድንቅ ነው! በሙዚቃህ ውስጥ ውብ ስሜት ይንፀባረቃል፤እባክህ ሙዚቃ መድረስህን ቀጥልበት፡፡ የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ነህ” በማለት አበረታቶታል፡፡ ታዋቂው አሜሪካዊ ፒያኒስትና አክተር ኒክ ሮልፍ በበኩሉ፤ “ወንድሜ፤እኔ የምመክርህ እየሰራህ ያለውን  እንድትቀጥልበት ነው፤ አዲስ ነገር እየፈጠርክ ነው” ሲል አድንቆ ፅፎለታል፡፡  
በአንድ ወቅት ከታዋቂው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ጋር የመገናኘት ዕድል ገጥሞት እንደነበር የሚናገረው ይስሃቅ፤ ግርማ ይፍራሸዋ የሰራውን ሙዚቃ በትዕግስትና በትኩረት ካዳመጠለት በኋላ፣ የማበረታቻ ምክር እንደለገሰው ጠቁሞ ባለውለታው እንደሆነ ይገልፃል፡፡
ወጣቱ የፒያኖ ተጫዋች ይስሃቅ ካሣሁን ገና የቀለም ትምህርቱን አላጠናቀቀም፡፡ በቦሌ ቃለህይወት የፕሪፓራቶሪ ተማሪ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርት ተሰጥኦውንና ችሎታውን የማሳደግ እቅድ እንዳለው ይናገራል፡፡ በተለይ በውጭ አገር ለመማር የስኮላርሺፕ ዕድል ቢያገኝ ምኞቱ ነው፡፡ እስከዛው ግን እየተደበቀ ይገባበት በነበረውና ፒያኖ መጫወት በተለማመደበት ኮርያ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሚገኘው “ጉድ ኒውስ ቸርች” የሙዚቃ ዳይሬክተር ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአንድ አልበም በላይ የሚሆኑ ሙዚቃዎችን እንደሰራ የሚናገረው ይስሃቅ፤ የራሱ ኦርጋን ፒያኖ ቢያገኝ ሙዚቃ የሚያቀነባብርበት ስቱዲዮ የመክፈት ሃሳብ እንዳለው ገልጿል፡፡ እስካሁን የሰራቸውን የሙዚቃ ስብስቦችም በአንድ አልበም የማውጣት ሃሳብ አለው፡፡ በእስካሁን ትጋቱ ከቀጠለ የስኬት ማማ ላይ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡


Published in ጥበብ

“በሰው ስራ ታውቆ የራስን መስራት ፈተና አለው”

ከጥቂት ዓመታት በፊት በዝነኛው ድምፃዊ ሙሉቀን መለሰ ሥራዎች ከአድማጮች ጋር የተዋወቀውና ተወዳጅነትን ያተረፈው አርቲስት ብዙአየሁ ደምሴ፤ በቅርቡ “ሳላይሽ” የተሰኘ የራሱን የመጀመርያ አልበም ለጆሮ አብቅቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየው ገበያው አልበሙ ከወጣ ጊዜ አንስቶ ድምፃዊውን ለማግኘት ስትታትር ቆይታ ባለፈው ረቡዕ ምሽት ተሳክቶላታል፡፡ ድምፃዊውን አሁን ከሚኖርበት ካናዳ በስልክ አግኝታው በአዲሱ አልበሙና በሙያው እንዲሁም በህይወቱ ዙሪያ እንደሚከተለው አነጋግራዋለች፡፡

ደህና አደርክ ልበል፣ ደህና ዋልክ? እኛ ጋ ከቀኑ አስር ሰዓት ነው...
ደህና አደርክ ነው የሚባለው፤ እኛ ጋ ከጠዋቱ 1 ሰዓት ነው፡፡ ግን አንቺ እንዴት ዋልሽ..?
በጣም ደህና ነኝ፡፡ አንተስ እንዴት አደርክ..ለነገሩ ድምፅህም የጠዋት ድምፅ ነው…
አዎ! ከእንቅልፌ እየተነሳሁ ነው፤ ጠዋት ስለሆነ ነው ድምፄ የጎረነነብሽ…እግዚአብሄር ይመስገን በጣም ደህና ነኝ፡፡ አገር ሰላም ነው? ሁሉ አማን? እኔ ሰላም ነኝ
ቤተሰብህን ጠቅልለህ ነው እንዴ ካናዳ የገባኸው..?
ቤተሰቦቼ ኢትዮጵያ ናቸው፤ ልጆቼም ባለቤቴም፡፡
በዚያው ቀልጠህ ቀረህ እኮ! ለመሆኑ አካሄድህ ለስራ ነው ለኑሮ?
ለነገሩ አሁን ሁሉ ነገር ስላለቀ መምጣት እችላለሁ፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት ለስራ ነበር የሄድኩት።
አዲሱ ‹‹ሳላይሽ›› አልበምህ እንዴት ነው? ተቀባይነት አገኘ? እስካሁን ምን ያህል ቅጂዎች ተሸጡ?
በትክክል ይሄን ያህል ኮፒ ተሸጧል ማለት መረጃው የለኝም፡፡ ነገር ግን ሙዚቃዬን ካሳተመልኝ የናሆም ሪከርድስ ባለቤት ጋር በየቀኑ እንገናኛለን፡፡ እንደ አሳታሚ ሳይሆን እንደጓደኞች ነን፡፡ እናም ባለቤቱ፤ “ብዙ አልበም ሰርቻለሁ፤ በዚህ ፍጥነት የተደመጠ ብዙ አልገጠመኝም”፤ ብሎኛል፡፡ እንዲህ በመሆኑም በጣም ተደስቻለሁ፡፡ የካናዳን ነገር ደግሞ ከምነግርሽ በላይ ነው፡፡ ሙዚቃው እንዴት እንደሚደመጥ አልነግርሽም፡፡ በቃ ያስደነግጣል .. ይሄን ያህል እደመጣለሁ እንዴ? ብዬ በእጅጉ ተደንቄአለሁ፡፡ አሳታሚዬ ናሆም ሪከርድስ ደግሞ አሜሪካ ነው ያለው፡፡ እሱ እንደነገረኝ እዚያም እጅግ በጣም ጥሩ ነው፤ ኢትዮጵያ ይደመጣል የሚባለው ያህል ሳይሆን አይቀርም ከፍተኛ ተ    ቀባይነት አግኝቷል፡፡
እስከዛሬ እንግዲህ በሰው ዘፈን ነበር የምትታወቀው፡፡ ከሰው ዘፈን ወደ ራስ ሥራ የመሸጋገሩ ሁኔታስ ምን ይመስላል? መቼም ፈታኝ እንደሚሆን እገምታለሁ …
አዎ፤ ከሰው ዘፈን ወጥተሽ የራስሽን ኦርጂናል ስራ ስትሰሪ በጣም ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም የራስ ዘፈን ሲሆን ራስሽን ሆነሽ ነው የምርቀርቢው። በተለይ በሰው ስራ ታውቀሽ ቆይተሽ የራስሽን ስትሰሪ ትንሽ ፈተና አለው፡፡
በአዲሱ አልበምህ ላይ በድምጽህም ሆነ በአዘፋፈን ዘይቤህ የሙሉቀን መለሰ ተፅዕኖ ጎልቶ እንደሚታይብህ ይነገራል፡፡ ይህን አስተያየት ትቀበለዋለህ?
አንዳንድ ጊዜ የምትወጅው ነገር የግድ ይስብሻል። ጥሩ ነገር ማን ይጠላል ብለሽ ነው… (ሳቅ)
የመጀመሪያ አልበምህ ሙሉ በሙሉ የሙሉቀን መለሰ ነበረ፡፡ ለአንዱ ዘፈን እንደውም የቪዲዮ ክሊፕ ሁሉ ሰርተህለታል፡፡ በዚህም ከሙሉቀን ጋር ተጋጭተህ ነበር፡፡ በአዲሱ አልበምህ ደግሞ አንድ የሙሉቀን መለሰ ዘፈንን ተጫውተሃል፡፡ አሁንስ አስፈቅደኸው ነው?
አዲስ የሰራሁት አይደለም፤ ከመጀመሪያ አልበም የተረፈ ነው፡፡ እንደውም መጀመሪያ ላይ ማካተት አልፈለግሁም ነበር፡፡ በኋላ የመጣ  ሃሳብ ነው፡፡ እሱም ቢሆን ግን ለኤሌክትራ ባለቤት እንዲሁም ለግጥምና ዜማ ደራሲዎቹ  አስፈላጊው ክፍያ ተፈፅሟል፡፡ ‹‹አትከብደኝም እስዋ›› የሚለውን ነው በአዲሱ አልበም ውስጥ ያካተትኩት፡፡
በነገርሽ ላይ አሜሪካ ሳለሁ ከጋሽ ሙሉቀን ጋር በጣም እንገናኝ ነበር፤ ካናዳ ከመጣሁ ነው የተጠፋፋነው፡፡ እና ለዚህ የሙሉቀን ዘፈን ብቻ የወጣው ብር በጣም ብዙ ነው…የናሆም ሪከርድስ ባለቤት አቶ ኤልያስ ነው የከፈለው፡፡
አዲሱ አልበምህ መለቀቁን ተከትሎ ከተለያዩ አገራት የኮንሰርት ጥያቄዎች አልቀረቡልህም?
አሁን በተጨባጭ ብዙ ስራዎች፣ ብዙ ኮንሰርቶች እየመጡልኝ ነው፡፡ አልበሙ በየቤቱ ይግባ እንጂ ሥራው ችግር የለውም፤ ይመጣል፤ ሰው ውስጥ እስኪዋሃድ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከፋሲካ በኋላ የኮንሰርት ጉዞዬን እጀምራለሁ፡፡ እስከዛ ግን ሁለት ነጠላ ዜማዎች እለቃለሁ፡፡ በተለይ አንዱ ነጠላ ዜማ በበዓል መዳረሻ ላይ ነው የሚሆነው፤ ያለቀ ስራ ነው፡፡
‹‹ሳላይሽ›› በሚለው አልበምህ ከህይወትህ ጋር የሳሰረ ዘፈን አካተሃል?
አዎ አለ፡፡ ‹‹የህልሜ ንግስት›› የሚለውን ለባለቤቴ ነው የዘፈንኩት፡፡ ከእግዚአብሄር በታች አጠገቤ ሆና ትረዳኝ የነበረች እሱዋ ነች፡፡ ‹‹ንገሪኝ›› የሚለውን ደግሞ ለእናቴ ነው የዘፈንኩት፡፡
አሁን ካናዳ ውስጥ በምን ስራ ነው የምትተዳደረው?
ሙዚቃ ነው የምሰራው፡፡ ከሙዚቃ ውጪ ምንም ነገር አልሰራም፡፡ ራሴን በሙዚቃው ዘርፍ ለማሳደግ ጥናቶች እያደረግሁ ነው፡፡ መተዳደሪያዬ ግን ሙዚቃ ነው፡፡
ለአዳዲሶቹ ዘፈኖችህ ቪዲዮ ክሊፕ ለመስራት አላሰብክም?
‹‹ሳላይሽ›› እና ‹‹ማመኔ›› ለሚሉት ዘፈኖች እዚህ ክሊፕ ሰርቼ እያለቀ ነው፡፡ በቅርቡ አድናቂዎቼ እጅ ይገባል፡፡
ቴዲ አፍሮ በስራህ እንደሚያደንቅህና ዝምድና እንዳላችሁ ሰምቻለሁ፡፡ ስለ አዲሱ አልበምህ አስተያየት ሰጠህ?
አዎ ዝምድና ነገር አለን፡፡ ዘፈኖቼን ብዙ የሰማ አልመሰለኝም፡፡ እስካሁን ምንም አይነት አስተያየት አልደረሰኝም፡፡
ካናዳ ለአርቲስቶች እንዴት ናት? ትመቻለች?
ውይ አትመችም፡፡ ከባድ ነው፤ እኔ እድለኛ ስለሆንኩ ነው፡፡ እዚህ ያለን አርቲስቶች የተወሰንን ነን፡፡ ሄኖክ አበበ፣ ፋንታሁን ሸዋንቆጨው፣ ይርዳው ጤናው፣ እና ሌሎችምሰ አሉ፡፡ ካናዳን እንደማረፊያ ነው የሚጠቀሙባት፤ የተለያዩ አገራት እየሄዱ ኮንሰርት እየሰሩ ይመጣሉ፡፡ ባለፈው ከአስቴር አወቀ ጋር ‹‹እንደ ወፍ›› በሚለው ዘፈን እየዞርኩ ኮንሰርት እንዳቀርብ አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ይኼንን አልበሜን ለመስራት አራት ዓመት ነው የፈጀብኝ፡፡ ትኩረቴ ሁሉ እሱላይ ነበር፡፡ አልበሜን ከዳር ሳላደርስ የትም አልንቀሳቀስም ብዬ ነው የቀረው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ኮንሰርት ለማቅረብ ሃሳብ የለህም? መቼ እንጠብቅ?
ኢትዮጵያ ላይ በቅርቡ አንድ ነገር ለማድረግ አስበናል፡፡ እስከዛው ለአድናቂዎቼ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ እንደምወዳቸው መልዕክት አስተላልፊልኝ፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ስላስተካከለልኝ አመሰግናለሁ፡፡ ባለቤቴ፣ ልጆቼ፣ አባቴን ጨምሮ አብረውኝ የነበሩትን ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡ ለዚህ አልበም በስኬት መጠናቀቅ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ አብረውኝ ለሰሩና ከጐኔ ላልጠፉት አማኑኤል ይልማና አቀናባሪ ወንድሜነህ ምስጋናዬ ይድረሳቸው፡፡ የናሆም ሪከርድስ ባለቤት አቶ ኤልያስንም በእጅጉ አመሰግነዋለሁ፡፡

Published in ጥበብ

          በኢትዮጵያ የህትመት ታሪክ ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞ የነገሰው የነፃው ፕሬስ ጉዞ፤ አስደማሚ ውጤት ለመፍጠር መቻሉ አያከራክርም፡፡ በአገራችን በተፈጠረው አንፃራዊ የዲሞክራሲ ጅማሮ የተነሳ በይፋ የተፈቀደው የነፃ ፕሬስ ህትመት፤ እንደጀማሪ ባህልነቱ ህፀፆች አልነበሩበትም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን፤ የንባብ ባህል እንዲደራጅ የነፃው ፕሬስ የተጫወተው ሚና፣ ልኬትና ወሰን አበጅቶ ከማስቀመጥ ይልቅ “ታሪካዊ ሚና” ቢባል ይሻላል፡፡
የነፃው ፕሬስ ህትመትን ማበብ ተከትሎ ወደ ሙያው ተቀላቅለው ድንቅ ስራዎችን እያበረከቱ ለህዝቡ በማስተዋወቅ፣ የንባብ ባህል እንዲደረጅ ያስቻሉ በርካታ ወጣት ጋዜጠኞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ብዙዎቹ በአድካሚው ሙያቸው፣ ፅናትን እንደ ትርፋቸው፣ ብርታትን እንደምንዳቸው፣ ተስፋን እንደ ጡረታ ዋስትናቸው ቆጥረው ይሰራሉ። በሙያው የከበረ ስምና ዝና ለማግኘት የቻሉ ወጣቶች የመኖራቸውን ያህል፤ ስራዎቻቸውን በመፅሐፍ መልክ አዘጋጅተው በማቅረብ ጠቀም ያለ ክፍያ ለማግኘት የበቁ ጋዜጠኞችም አልጠፉም፡፡  እጅግ ብርቱ ፈተና በሰፈነበት፣ ፅናትና ቁርጠኝነት ወሳኙ ሀይል በሆነበት የነፃው ፕሬስ ዓለም ውስጥ የገጠማቸውን ሁሉ በትዕግስት ችለው፣ ሙያዊ ብቃታቸውንና ዕውቀታቸውን ለህዝባቸው ሲመግቡ ቆይተው፤  የመፅሐፍ ዓለሙን ጎራ የተቀላቀሉ የብዕሩ ዓለም ቤተኞችን ለማየት መብቃታችን እሰየው አሰኝቶናል፡፡
የመፃህፍት ህትመት ከቅርብ አመታት ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ታሪክ ውስጥ አይነተኛ ቦታ የነበራቸው ጋዜጠኞች የካበተውን ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለህዝባቸው የሚያካፍሉበትን ተጨማሪ መድረክ ያመቻቸም ሆኗል፡፡ ከእነዚህ የነፃው ፕሬስ ባለሙያዎች መካከል ጋዜጠኛ አብነት ታምራት አንዱ ነው፡፡ የመፅሐፍ ንባብን እንደ ቀለብ ለሚቆጥሩ ብቻ ሳይሆን፤ እግር ኳስን እንደ መሰረታዊ ጉዳይ ለሚከታተሉ  ኢትዮጵያዊያን በአይነቱ ለየት ያለ መፅሐፍ ለህትመት አብቅቷል፡፡
መፅሐፉ
ጋዜጠኛ አብነት፤ ‹‹አርሰናል›› የተሰኘው መፅሐፉን ያዘጋጀው የረጅም ጊዜ የጋዜጣ ዓለም ዕውቀትና ልምዱን ተጠቅሞ ነው፡፡ ስለ አርሰናል ክለብ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች፣ መዛግብትና መፅሐፍት አሰባስቦ፤ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ፣ እጅግ ባማረ ቋንቋ እያሰናሰለ ለንባብ አቅርቦታል። በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ ሁነኛ ስፍራ ያለውና በኢትዮጵያዊያን ስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት የተቀዳጀው አርሰናል የእግር ኳስ ክለብ፤ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስከደረሰበት ደረጃ  አሳምሮ ይተርካል - መጽሐፉ፡፡
የአርሰናል ምስረታ ከተጠነሰሰበት ውልዊች ጀምሮ አሁን እስከደረሰበት ኤምሬትስ ድረስ ያለው ታሪካዊ ጉዞ ማራኪ ቢሆንም፤ የመፅሐፉ  አዘጋጅ የዚህን ክለብ ማራኪ ታሪክ ለማስነበብ የተጠቀመበት የትረካ አፃፃፍ ያስገርማል፡፡ የክለቡን ታሪክ በአምስት ምዕራፎችና በተለያዩ ንዑስ አንቀፆች ከፋፍሎ በቅደም ተከተል በማስቀመጥ መፅሐፉን ያለእፎይታ እንድናነበው አድርጓል፡፡
በ219 ገፆች የቀረበው የክለቡ ታሪክ፤ ከታሪክ ማጣቀሻነቱ በዘለለ እንደ አንድ የስነፅሁፍ ልምድ መፍጠሪያ መፅሐፍ እንዲቆጠር ፀሐፊው የተጠቀመበት ስልት አስደናቂ ነው፡፡ ፀሐፊው በሜዳ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተጨዋቾች ያደረጓቸውን የአንድ ወቅት እንቅስቃሴዎች ብቻ ሳይሆን፤ ያስቆጠሯቸውን ምርጥ ግቦች አስፍሮ ለአንባቢ ለማስረዳት የተጠቀመባቸው የምስል አተራረክና አገላለፅ ጥበቡ፤ የጀመርነውን ምዕራፍ ካነበብንም በኋላ የአፃፃፍ ስልቱንና ብቃቱን ለመመርመር  ተመልሰን እንድናነብ ያስገድደናል፡፡ የላቀ የንባብ ፍላጎት ያላቸው መደበኛ አንባቢዎችን ብቻ ሳይሆን፤ አማራጭ ስላልቀረበላቸው ብቻ ከንባብ ርቀው በመቀመጥ፣ የእግር ኳስ መረጃዎችን ብቻ በማነፍነፍ ተጠምደው የሚውሉ የስፖርት አፍቃሪዎችን ወደንባብ እንዲሳቡ ይጋብዛል፡፡
በተለያዩ ዘዴዎች ተበታትነው የሚታዩትንና በሳምንታዊ ጋዜጣዎች ላይ ጊዜ እየጠበቁ  ለንባብ የሚቀርቡትን የክለቡን መረጃዎች እየለቀሙ ማንበብ፣ ለክለቡ የልብ ደጋፊዎች፣ ለእግር ኳስ አፍቃሪዎችና ለንባብ ባህል አራማጆች ብዙም ፋይዳ ያለው ባለመሆኑ ለንባብ በበቃው ‹‹አርሰናል›› መፅሐፍ በአንድ መድበል ተካቶ መቅረቡ ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡
የመፅሐፉ ግብ
 በመግቢያው  ላይ መፅሐፉ ለኢትዮጵያዊያን ስፖርት አፍቃሪዎች የሚሰጠው ጠቀሜታ እጅግ ባጠረና በተመጠነ መልኩ ቀርቧል፡፡ ይሁንና የመፅሐፉ አጠቃላይ ጉዞ በዚሁ እንዲያከትም በማድረግ ግቡን አሳንሶ  መተመን አግባብ አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ የዚህ ታላቅ ክለብ ተመክሮ ለኢትዮጵያዊያን ታላላቅ ክለቦች የሚሰጠው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡ ክለባዊ መዋቅርና አደረጃጀቱ በጥልቀት አለመቅረቡ በመፅሐፉ ላይ የሚታይ አንድ ደካማ ጎን መሆኑ ባይካድም፤ በዝርዝር ከተቀመጡ ነጥቦች በመነሳት የመፅሐፉ ጠንካራ ጎን ሚዛን ይደፋል ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
በመፅሐፉ ላይ ከተቀመጡት አንኳር ነጥቦች መካከል ስለክለቡ ደጋፊዎች የተቀመጠው ዝርዝር በበኩሉ፤ ጉዳዩን ወደእኛ እውነታ በማምጣት ለመዳሰስ አለመሞከሩ ቅር ያሰኛል፡፡ መፅሐፉ ታላላቅ የተባሉ የክለቡ ደጋፊዎችን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ልዕልት ኤልሳቤትና ልዑል ሃሪ ከንጉሳዊያን ቤተሰቦች የተጠቀሱ ሲሆን ኬቨን ኮስትነር፣ ማት ዴመንና ዴሚ ሙር ከፊልም አክተሮች፤ ሬይ ዴቪስና ጄይ ዚ ከሙዚቀኞች፤ ዳረን ቤንት፣ ሞ ፋራህ፣ ቲዬሪ ሆንሪ፣ ራፋኤል ናዳል፣ ሀሪ ሬድናፕ፣ ፍብሪጋዝ፣ ዲያጎ ማራዶናና ዴኒስ ቤርካምፕ ከስፖርተኞች እንዲሁም ፖል ካጋሜ ከፖለቲከኞች ከተዘረዘሩ በርካታ ታላላቅ ሰዎች መካከል ስማቸው ተጠቅሷል፡፡
ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን ፖለቲከኞች፣ ባለሀብቶች፣ የስፖርት ሰዎችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሰፊ ድጋፍ የሚሰጡት አርሰናል፤ በኢትዮጵያዊያን በኩል ያለው ገፅታ ምን መልክ እንዳለው ለማሳየት የእነዚህ ታዋቂ ሰዎች ዝርዝር መካተት ነበረበት፡፡ ከዚህ አንፃር መፅሐፉ ክፍተት ስለሚታይበት ደራሲና ጋዜጠኛ አብነት ታምራት ይሄንን  ለመሙላት በቀጣይ ክፍል ስራው ትልቅ ጥረት ማድረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ፀሃፊው፣ የኢትዮጵያዊያን ታላላቅ ሰዎችን ዳራ በመተንተን፣ ከአርሰናል ክለብ ጋር ያላቸውን ቁርኝትና ለክለቡ ያላቸውን ፍቅር በጥልቀት ቢዳስስ ኖሮ፣ መፅሐፉን የበለጠ አገርኛ ቅርፅ እንዲኖረው ማድረግ ይችል ነበር፡፡
ከዚህ የአብነት የብዕር ትሩፋት በመንደርደር፣ ሌሎች ስፖርት ተኮር አገርኛም ሆነ የባህር ማዶ መፃህፍት ለንባብ እንደሚቀርቡ እምነቴ ነው። ምክንያቱም የንባብ ባህልን ማሳደግ የሚቻለው ለንባብ የሚቀርቡ አማራጮችን በማስፋት መሆኑ አያነጋግርምና፡፡
ሌሎችም ይሄ ፀሃፊ የጀመረውንና ለአንባቢው ትውልድም ሆነ ለስፖርት አፍቃሪው አማራጭ ይዞ ብቅ የማለት ይትበሃልን ገፍተውበት፣የአለማችን ምርጥ የስፖርት ጀግኖችን ታሪክ ለትውልዱ የሚያቀርቡበትን መስመር ከወዲሁ መተለም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋርና ወርቅነሽ ኪዳኔ የመሳሰሉ ጀግና ኢትዮጵያዊ አትሌቶችን ታሪክ በመጽሐፍ አትሞ በማቅረብ፣ ትውልዱ ከእነሱ ጀግንነት የጠለቀ ትምህርትን እንዲያገኝ ማድረግ ጠቃሚ ስለሆነ፤ የመስራት አቅሙና ብቃቱ ላላቸው ፀሐፊዎች ሁሉ “አርሴናል” የማንቂያ ደወል እንደሚሆናቸው እምነቴ ነው፡፡    

Published in ጥበብ

ዝነኛዋ ባለቅኔ እመት ገላነሽ አዲስ በ1974 ዓ.ም ሠዓሊ ዘውዱ ኃይሌ
ፐርትሬታቸውን እንደሠራው
በደብረጽላሎ አማኑኤል ገዳም የሚገኘውና በመፈራረስ ላይ ያለው
የእመት በላይነሽ አዲስ መቃብር
በደብረጽላሎ ገዳም እመት ገላነሽ ካረፉ በኋላ የቅኔ ጉባኤያቸው እንዳይፈታ ቅኔ ሲያስተምሩ የነበሩት መሪጌታ አበራ ብርሃኑ


በኢትዮጵያ የቅኔና የባለቅኔ ታሪክ ሲነሣ እመይቴ ገላነሽ ሐዲስ የማይዘነጉ የቅኔ ንግሥት ሆነው በአእምሮዋችን ውስጥ ይመላለሳሉ። እኒህ የቅኔ ንግሥት ምንም እንኳን የዓይን ብርሃናቸውን አጥተው ለመኖር ቢገደዱም ዓይናማዎች ከሚያደርጉት በላይ በሕይወታቸው በዚያ በጨለማው ዘመን አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ፈጽመው አልፈዋል፡፡
እመይቴ ገላነሽ የባለቅኔዎችን ሐሳብ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ ስለነበራቸው፣ከአባታቸው ከቄሰ ጎበዝ ሐዲስ ኪዳን ጀምሮ የብዙ ባለቅኔዎችን ቅኔ በእሳቤ እየደረሱበት ነጥቀዋቸዋል፡፡ ከብዙ ባለቅኔዎች ጋር እንቆቅልሽ ቅኔ በመላላክ ቅኔያቱን በምርምር ፈትተዋል፡፡ በተለይ ከቦገና ግራሩ የቅኔ መምህር ከጥበቡ ካሣ ጋር ምሥጢር ያለው ቅኔ ይላላኩ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከእንቆቅልሽ ቅኔዎቻቸው ውስጥ
ሐወፀ ሮጌል ወወልደ ነጐድጓድ መዋቲ፡፡
ክሳድየ እኁብ እመ ትፈትሐ ለዛቲ፡፡
ይህንን ቅኔ ወልደ ነጐድጓድ ሟችን ሮጌል ጐበኘው፡፡ ይህንን ከፈታህ አንገቴን እሰጣለሁ ብሎ በጥሬው ሰው ሊፈታው ይችላል፡፡ ግን ትርጉሙ ይህ አይደለም፡፡
ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድና መቃብር (ሮጌል) እንደ ሀና ጸ የተራራቁ ናቸው ማለት ነው፡፡ ወልደ ነጐድጓድ ዮሐንስ ሞቶ ግን ወደ መቃብር ያልገባ መሆኑን እንቆቅልሹ ያስረዳል፡፡
በመጨረሻ እመይቲ ገላነሽና መምህር ጥበቡ በእንቆቅልሽ ቅኔ ሲፈታተሹና ሲመላለሱ ኖረው በመጨረሻ እመይቴ ገላነሽ ሳይፈቱት የቀረ የጥበቡ ቀጣይ ቅኔ አለ፡፡
ይኸውም “ሞቶን ሞተኪ ሞተ ፈጣሪ ገላም ገላነሽ ይህንን ፈትተሽ ፈክሪ” የሚለው ነው፡፡
የቅኔ ተማሪዎቻቸውና አስነጋሪዎቻቸው ዘራፊዎቻቸው ሲቀኙም መጨረሻውን እንዲህ ለማለት ፈልገህ ነው አይደል! ብለው የቅኔውን ምሥጢር እየደረሱበት ሲያስተካክሉ ኖረዋል፡፡ ግስን እየተነተኑና ቅኔን እየዘረፉ በቅኔ ሙያቸው ለ50 ዓመት አስተምረዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ፈትል ሲፈትሉ፣ ስፌት ሲሰፉ ተወዳዳሪ አልነበራቸውም ይባላል፡፡ የፈተሉት ፈትልና የሰፉት ስፌት በሁለት ሺህ ዓ.ም እርሳቸውን የሚዘክር በዓል ባሕርዳር ላይ ተዘጋጅቶ በነበረበት ጊዜ ለዕይታ በቅቷል፡፡
ለአንድም ቀን ቤተ ክርስቲያን ቅኔ ማኅሌት ገብተው ቅኔ ባለመቀኘታቸው ይቆጩ የነበሩት እመይቴ ገላነሽ፤ ይህንኑ ጾታዊ እኩልነት ያልነበረውን ጽልመታዊ አሠራር እንዲህ በማለት ነቅፈውታል፡፡ ቅኔው ሥላሴ ነው፡፡ (አድማሱ ጀንበሬ) ዝክረ ሊቃውንት 1963)
ለብእሲት በዊኦታ
ውስተ ቤተ ማኅሌት ጊዜ ማኅሌት
ኢኮነ ነውረ አመ ሊቃውንት ሐተቱ
ማኅሌት እስመ እምቀዲሙ ለብእሲት ውእቱ።
ካህናትሰ ኪያየ ይእዜ ለእመ ከልሁ በከንቱ፡፡
ብዙኃ ነውረ ከመ ይከብቱ፡፡
አኮኑ ገቢረ እምተገብሮቱ፡፡
ኢፈለጡ ወቤተ ነሠቱ፡፡
ትርጉም፡ በማኅሌት፣ በጭብጨባ፣ በዘፈን ጊዜ ሴት ወደ ማኅሌት ብትገባ ነውር አይደለም  ዝማሬ ዘፈን እልልታ ጭብጨባ ቀድሞውንስ ቢሆን ለሴት ነውኮ፡፡
 ብዙ ነውር የሚሰበስቡት ካህናት ግን በእኔ ላይ በከንቱ ቢጮሁብኝም  ገቢር ተገብሮ/አገባብ/የቅኔ አገባብ/ስለማያውቁ ቤቱን እያፈረሱት ነው፡፡
ይህ ቅኔ መራርነት ያለውና የሴትነትን ስሜት የሚነካ ነው፡፡ እኒህ የቅኔዋ ንግሥት ሐዋርያው ጳውሎስንም ይተቹታል፡፡ ጳውሎስ ሴቶችን አስመልክቶ ሲያስተምር “አንስትሰ ይትገልበባ ርእሶን ለእመ የሐውራ ውስተ ቤተ መቅደስ” (ሴቶች ወደ ቤተ መቅደስ ሲሔዱ ራሳቸውን ይሸፋፈኑ ብሏል) በጉባዔም እንዳያስተምሩ ከልክሏል፡፡ ይህንን የሴት ተቆጭ ሐዋርያ እመይቴ ገላነሽ በመወድስ ቅኔያቸው ለመርታት እንዲህ ይሉታል፡፡
መገስጸ አንስት ጳውሎስ በቃለ ተግሳጽ
ለእመ ይቤ ኢትምሀር ብእሲት በጉባዔ፡፡
ለዘራዔ ንባብ ጳውሎስ ኢንሬስዮ ሠራዔ፡፡
ሥርዓተ ብእሲት ባሕቲታ
በብእሲት አምጣነ ተነግረ መወድስ ትንሣኤ፡፡
ወከመ ይስብኩ መወድሰ
ገላነሽ ፈነወት አርድእተ በበክልኤ፡፡
ጳውሎስሂ ለእመ ሰምዐ ዜና ዲቦራ መጽንዔ፡፡
እምኢኮነ ለአንስት መገሥጸ ወከላኤ፡፡
ዲቦራ እምነ እስመ ወውዐት ውዋዔ፡፡
በቅኔ ወበመዝሙር በቅድመ ጉቡአን ሰብአ.ጽዋዔ፡፡  
(አድማሱ ጀንበሬ ዝክረ ሊቃውንት 1963 ገጽ 306-307)    
ትርጉም፡ ሴቶችን በመቆጣት በመገሰጽ የሚታወቀው ጳውሎስ፤ በጉባዔ ሴት አታስተምር ቢልም ንባብ የሚዘራ ጳውሎስን እንደሠራ አንቆጥረውም፡፡ መወድስ ትንሣኤ የተነገረው እኮ በሴቶች  ነውና፡፡ (ማርያም መግደላዊት ስለጌታችን  ትንሣኤ አስቀድማ ስለአበሠረች ነው)፡፡
መወድስን ይሰብኩና ያስተምሩ ዘንድ ገላነሽ ሁለት ሁለት እያደረገች ተማሪዎችን ልካለች፡፡
ጳውሎስ አጽናኙ የሆነውን የዲቦራ ዜና ቢሰማ፣ የሴቶች ተቆጭና ጩዋሂ ባልሆነም ነበር፡፡
ዲቦራ እናታችን በቅኔና በመዝሙር በተጠሩ  በተሰበሰቡ ሰዎች ፊት ጩኸትን ጮሃለችና፡፡
እመይቴ ገላነሽ፤ሐዋርያው ጳውሎስን በዚህ ዓይነት መንገድ ሞግተውታል፡፡ ጳውሎስን የተቹት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እማሆይ ገላነሽ የግዕዝ ቅኔ መምህርት ሆነው ለ50 ዓመታት በማስተማር ሲኖሩ በሴትነታቸው ምክንያት አንድም ቀን እንኳን በቤተክርስቲያን ውስጥ ቅኔ ተቀኝተው አያውቁም ነበር፡፡ ይቀኙ ብሎ የጋበዛቸው ካህንም አልነበረም፡፡ ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት ከላይ እንደተገለጠው ሐዋርያው ጰውሎስ ሴት በጉባኤ ወይም በማኅበር  አታስተምር ብሎ በመናገሩ ነው።
እኒህ ዝነኛ ባለቅኔ እግዚአብሔርንም እንዲህ በማለት ይሞግቱታል፡፡
ሚበዝኁ ዘእማሆይ ገላነሽ (አድማሱ 1963 ገጽ 148)
ይእዜ አእመርኩ ከመ ኢይፈትሕ ካዕበ እግዚአብሔር ሊቀ ፈታሕት፡፡
እመ ከደኖን ጽልመተ ለእለሥጋዬ አዕይንት፡፡
እስመ ረሰየ ይርአያ አዕይንትየ ዘውስጥ ምሥጢራተ ቅኔ ክቡት፡፡
ትርጉም፡ የፈራጆች ፈራጅ እግዚአብሔር በትክክል እንደማይፈርድ ዛሬ አወቅሁ፡፡ የፊት ለፊት ዓይኖቼን አጥፍቶ ሸፍኖ በውስጥ ዓይኖቼ ግን የቅኔ ምሥጢርን እንዳይ አድርጓልና፡፡
እማሆይ ገላነሽ፤በምዕራብ ጎጃም ውስጥ በቀድሞ አጠራሩ ይልማናና ዴንሣ ወረዳ በአሁኑ አጠራር በጎንጂ ቆለላ ወረዳ በጽላሎ አማኑኤል ገዳም በ1898 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ አባታቸው ቄሰ ገበዝ ሐዲስ ኪዳን ይባላሉ፡፡ እናታቸው ደግሞ  ወ/ሮ ወርቅነሽ እንግዳ ይሰኛሉ፡፡ በስምንት ዓመታቸው በኩፍኝ በሽታ ምክንያት የዓይን ብርሃናቸውን አጥተዋል ነገር ግን ይህ የአካል ጉድለት የአእምሮአቸውን ብሩህነት ሊገታው ስለአልቻለ በልጅነታቸው ከአባታቸው ከቄሰ ገበዝ ሐዲስ ኪዳን ዘንድ ውዳሴ ማርያምን፣ ቅዳሴ ማርያምን፣ መልክዐ ኢየሱስንና መልክዐ ማርያምን፣ መዝሙረ ዳዊትን በቃላቸው አጥንተዋል፡፡ ቀጥሎ ቅኔ ከነጓዙ ከአባታቸው ዘንድ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜንም ተከታትለዋል፡፡
እማሆይ ገላነሽ የቅኔ መምህርት ሆነው ከተመረቁ ጊዜ ጀምሮ አባታቸው እስከ ዐረፉበት 1928 ዓ.ም ድረስ የአባታቸው ረዳት መምህርት ሆነው ሲያስተምሩ ኖረዋል፡፡ ከአባታቸው ዕረፍት በኋላም የቅኔ ጉባኤውን ተረክበው ተወልደው በአደጉበትና ተምረው ለመምህርነት በበቁበት በደብረ ጽላሎ አማኑኤል ገዳም ለ50 ዓመታት ቅኔን አስተምረዋል፡፡ ያረፉት ሐምሌ 11 ቀን በዕለተ ሐና ሲሆን ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመው ሐምሌ 12 ቀን 1978 ዓ.ም ነው፡፡ ዐጽማቸው ያረፈውም በደብረ ጸላሎ ገዳም ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የመቃብራቸው ሁኔታ በፎቶግራፍ ላይ የሚታየውን ይመስላል፡፡
እመት ገላነሽ በደብረ ጽላሎ ቅኔ መምህራን ተዋረድ 55ኛዋ ሲሆኑ ባለትዳርም ነበሩ፡፡ ባለቤታቸው አቶ ጥሩነህ ኪዳነማርያም ፈረሰኛ ነበሩ፡፡ እመት ገላነሽ ከአቶ ጥሩነህ ሦስት ልጆችን ወልደዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው መሪጌታ አዳም ኪዳነማርያም ይባላሉ (በአያታቸው ስለሚጠሩ ነው፡፡) ሁለተኛዋ ወ/ሮ መሠረት ጥሩነህ ሲባሉ ሦስተኛ ልጃቸው እንደተወለደ ሞቶባቸዋል፡፡
መሪጌታ አዳም ጎንደር ውስጥ የዐደባባይ ተክለ ሃይማኖት የመጽሐፍ መምህር ነበሩ፡፡ እርሳቸውም ሰባት ልጆችን ወልደው በድንገት አልፈዋል። ከመሪጌታ አዳም ልጆች፣ ሰብለ ወንጌል አዳም ውጭ አገር ስትሆን ሌላዋ ሐመልማል አዳም አዲስ አበባ ውስጥ እንደምትገኝ መሪጌታ አበራ የእመት ገላነሽ የልጅ ልጅ ባለቤት አጫውተውኛል፡፡
እመት ገላነሽ ሐዲስን የምናስታውሳቸው በቅኔ ሙያቸው ቢሆንም መልካም ዘር ተክተው በማለፋቸው ጭምር እንዘክራቸዋለን፡፡ የእርሳቸው ልጅ ወ/ሮ መሠረት ጥሩነህ እውነትም መሠረት ያላቸው ናቸው፡፡ ከእርሳቸው አብራክ ሙሉነሽ፣ አስረሳሽ፣ አጀቡሽ፣ ውባለች፣ ኃይሉና በያብልብኝ ተገኝተዋል፡፡ ወ/ሮ ሙሉነሽ ደግሞ /የእመይቴ ገላነሽ የልጅ ልጅ/ መሪጌታ አበራ ብርሃኑን አግብተው ሰገነትን፣ ደጊቱን፣ የትምወርቅን፣ ዘውዲቱን፣ ቤተልሔምንና ኪዳኑን ወልደዋል። እነዚህ ሁሉም የመሪጌታ አበራ ብርሃኑ ልጆች ሲሆኑ ኪዳኑ አበራ በአሁኑ ሰዓት የእመት ገላነሽን የቅኔ ጉባኤ ተክተው፣ ቅኔን በደብረ ጽላሎ አማኑኤል በማስተማር ላይ ናቸው፡፡
ወጣቱ ኪዳኑ አበራ በቅኔ መምህርነት ማዕረግ ከመመረቃቸው በፊት የእመት ገላነሽ ጉባዔ እንዳይፈታ ሲያስተምሩ የነበሩት አባታቸው መሪጌታ አበራ ብርሃኑ ናቸው፡፡ እርሳቸው በአሁኑ ሰዓት ስለደከሙ መምህር ኪዳኑ አበራ በቅኔ ሙያ እስኪመረቁ ድረስ የጉባዔው መምህር የነበሩት የገዳመ አስቄጥስ ተክለሃይማኖት ወክርስቶስ ሠምራ የቅኔ መምህር የሆኑት ዘለዓለም ተድላ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል የእመት ገላነሽ የቅኔ ጉባዔ የነበረው ቤተክርስቲያኑ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን የቅኔ ቤቱ የተደራጀው ራቅ ብሎ ለተማሪዎች ኑሮ የተመቸ ሆኖ ነው፡፡ ቅኔ ቤቱ ከአንድ ትልቅ ዋርካ ዛፍ አጠገብ የሚገኝ ሲሆን በአብዛኛው በሳር ቤት የተሠራ ነው፣ የቅኔ ጉባኤውም ሳር ቤት ነው፡፡
በደብረ ጽላሎ በአሁኑ ሰዓት ሦስት ቅኔ መምህራን አሉ፡፡ እነርሱም መምህር ኪዳኑ አበራ፣ ለዓለም ብርሃኑና ክቡር አደራው ናቸው። የመምህር ኪዳኑ ዘሮች እስከ ዐስር ትውልድ ደርሰዋል። (በቅኔ መምህርነት ማለት ነው) ዐሥረኛው መምህር ኪዳኑ አበራ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ገና የ24 ዓመት ወጣት ሲሆኑ ትዳር የመሠረቱትም በቅርቡ ነው፡፡
የደብረ ጽላሎ የቅኔ ጉባዔ በእመት ገላነሽ ስም የተሰየመ ሲሆን ጽርሐ ጽዮን ይባላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እስከ 200 የሚደርሱ የቅኔ ተማሪዎችም  ይኖሩበታል፡፡   


Published in ጥበብ

እነሆ ወርሃ የካቲት መጣ፡፡
አበቦች አንገታቸውን ማስገግ የሚወዱበት ወቅት ነው፡፡ የሚኳኳሉበት፡፡ ከብጤዎቻቸው ይበልጥ አምረው ደምቀው ይመረጡ ዘንድ የሚዋትቱበት፡፡ “እኔን! እኔን!” የሚሉበት፡፡ አበቦች እንደዚህ ወቅት ተወዳጅ የሚሆኑበት ጊዜ ይኖር ይሆን?
የፍቅረኞች የመሽሞንሞኛ ቀን “ቫለንታይንስ ዴይ” ሰሞኑን ተከበረ አይደል! ከአንዱ ዓመት ወደ ሌላኛው እንደምን እየሰፋ፣ እየተንሰራፋ፣ እየገዘፈ እንደመጣ ለማስረገጥ ምስክር ጥራ አልባልም መቼም፡፡ ግድየለም የቢዝነስ ጋዜጦቻችን የስጦታ ገበያ ሸመታውን አስልተው፣ ከቀድመው ጊዜ ጋር አነጻጽረው ይነግሩናል፡፡ የሬዲዮ አሰናጆች ድምጻቸው አለሳልሰው፣ ሙዚቃቸውን አቀዝቅዘው የዕለቱን አዋዋል በተለይ ደግሞ አመሻሽ አትተውልናል፡፡ እኔ ግን “እባካችሁ --- የአምልኮተ- ሮማንስ ሩጫችሁን ቀንሱ!” እላለሁ፡፡
በመጀመሪያ ማጥራት ያለብን እሳቤ አለ፡፡ (አንድ ሰሞን ፈሊጥ እንደነበረው “ፍቅር አለ ወይስ የለም?” የሚል ሞኛሞኝ ክርክር ውስጥ ራሴን መዶል አልፈልግማ!) የቃላት አጠቃቀሙ በራሱ ችግር ያለበት ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው አንዲት ቀዘባ እና ወዳጇ የሚጀመሩትን ፍቅር ነክ ግንኙነት ለመግለፅ love፣ relationship፣ dating  የተባሉ ቃላትን እያቀያየሩ  መጠቀም ተለምዷል፡፡ (“የከንፈር ወዳጅ” ይሏት ሀረግ ግን ትርጉሟ ተምታቷል እንጂ እንደምን ገላጭ ናት!) የኋለኞቹ ሁለት ቃላት (dating እና relationship) romance  በሚባለው ኮሮጆ ሊቋጠሩ የሚገባቸው ናቸው፡፡ እና በlove እና romance መካከል ትልቅ የትርጉም ልዩነት አለ፡፡
Love ጠሊቅ ነው፡፡ ረጅምም ነው፡፡ ጓደኝነት ነው፡፡ ንብቡነት ነው፡፡ አገልግሎት ነው፡፡ ተረት የሚመስል ስሜት አይደለም፡፡ እናት ወህኒ የወረደ ልጇን ለአፍታ እንኳ ቅያሜ ሳትይዝበት፣ለአንድም ቀን ሳታዛንፍ ተመላልሳ ስትጠይቀው እናያለን። አባት ግላዊ ምቾቱን ትቶ ከንጋት በፊት ከቤት ወጥቶ ሲፍገመገም እየዋለ፣ ማታውን ደግሞ ከልጆቹ ጋር ሲጫወት ለማምሸት ተብከንክኖ እቤቱ በጊዜ ይገባል፡፡ ባለትዳሮች ለሰላሳና አርባ አመታት ህመም እና ፈውሳቸውን ሲጋሩ እናስተውላለን፡፡ በጋሽ ስብሃት አጭር ታሪክ “ዔሊን ድንጋይ ያለበስክ” ላይ በአሮጊቷ በኩል የሚነገር ነው፡፡ (“ለምን ይለምናሉ?” ብሎ ጠየቃቸው ተራኪው አሮጊቷን። ልጃቸውን ብለው ተንከራተቱ፡፡ ልጃቸው አድጎ ሲያገባ ሚስቱ ጠላቻቸው፡፡ አሮጊቷ ልጃቸውን ፈተና ውስጥ ሊከቱት አልሻቱም፡፡ እርሱም አሁን ወልዷል፡፡ የልጁን ፍቅር ያውቁታል፡፡ ስለዚህ ሹልክ ብለው ወጡለት፡፡) ትንንሽ የሚመስሉ ትልልቅ መስዋእትነቶች ድምር ነው - love
Romance በአንፃሩ ይሄንን ሁሉ አይደለም። የሆሊውድ የእጅ ሥራ ነው (በርግጥ አንድሩ ሱሊይቫን የተባለ እና ከአስራ ምናምን ዓመታት በፊት በኒውዮርክ ታይምስ መፅሄት ላይ “The Love Bloat” የሚል ርዕስ ያለው መጣጥፍ ያሳተመ ፀሃፊ እንደሚለው፣ ሮማንስን  የፈጠረው ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሩሶ ነው፡፡ ወደ እርሱ መመለሴ አይቀርም።) ሮማንስ ቀመር አለው፡፡ ቀመሩን አምርቶ ለዓለም ህዝብ ሁሉ የሚያስተምረው ደግሞ ሆሊውድ የተባለው ተረት አምርቶ የሚተዳደር ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በቀመራዊ የሮማንቲክ ኮሜዲ ፊልሞች። (ሆሊውድና የአሜሪካ የሸማችነት ባህል ይሄንን አምልኮ ባይፈጥሩትም የተለጠጠ ፋይዳውን በመፍጠር ግን የድርሻቸውን ሚና እንደተጫወቱ አያጠራጥርም) አሁን ልፋቱ ሁሉ ተሳክቶለት የመላው ዓለም ወጣቶች፣በአምልኮተ ሮማንስ ተሰልበው ሲሸነጋገሉ ያመሻሉ፡፡ በሆሊውድ በተደረሰው ማኒፌስቶ መሰረት፣የሮማንስ መገለጫዎች የማያሻሙ ናቸው፡፡ አንዲትን ሴት ለdate መጠየቅ - ብዙ ጊዜ የራት ግብዣ ነው፡፡ ምርጥ ምግብ ቤት መመረጥ አለበት፡፡ በተቻለ መጠን ያንን ምሽት እንስቷ ተረት በሚመስል ስሜት ውስጥ ተንሳፋ እንድታሳልፈው እንዲያስችላት ይጠበቃል ከወንዱ። ልክ ለስራ ቅጥር የሚደረግ ፈተና የሚመስል አይነት ነገር አለበት፡፡ ከተሳካለት እና ምሽቱ በሚገባ ካለፈ ቤት ድረስ ይሸኛታል፡፡ ይስማታል፡፡ እና “ድንቅ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፣ አመሰግናለሁ” ይባባላሉ። ከዚያ ለጓደኞቻቸው “We are dating” ወይንም “We are seeing each other” ይላሉ፡፡ Love የምትባለውን ቃል ለረጅም ጊዜያት ምናልባትም ለወራት እና ዓመታት አይጠቀሙባትም፡፡ ወንድየው የልደት ቀኗን መርሳት የለበትም፡፡ የምትነግረውን ዝባዝንኬና እንቶ ፈንቶ ሁሉ ማዳመጥ አለበት፡፡ ደግሞ የተረት ተረቱ የመጨረሻው  ደረጃ (ጡዘት) በወርሃ የካቲት ይመጣል፡፡ የቅዱስ ቫላንታይን ቀን፡፡ አበባው ይገዛል፡፡ ወደ ምግብ ቤት ሄዶ ራት ይበላል፡፡ ስጦታም ይበረከታል፡፡ ከዚህም የተሻገረ ነገር ይኖራል፡፡ ሽርሽር ይሰናዳል፡፡ የ”አግቢኝ” ጥያቄ ይጠበቃል፡፡ ደግሞም ጥያቄው ድራማዊ መሆን አለበት፡፡ ይሄ የማይዛነፍ ቀመር የሚጠቅመው እንግዲህ የፊልም አምራቾችን፣ የምግብ ቤት ባለቤቶችን፣ የስጦታ እቃ ሻጮችን እና አበባ ነጋዴዎችን ነው፡፡ እነርሱም ለዕለቱ በሚገባ ነው የሚዘጋጁት፡፡ በዕለቱ ያለ ተጣማሪ መሆን የብቸኛነት ትርጉም ተደርጎ ይታሰባል፡፡
ልዩነቱ ግልጽ ነው፡፡ Love is authentic, Romance is counterfeit. ፍቅር ቱባ ነው። ሮማንስ ቅጂ፡፡ (ዲ.ኤች.ሎረንስ “Lady Chatterley’s Lover” ለተባለው አወዛጋቢ ልቦለዱ ማብራሪያ ይሁን ብሎ በፃፈው መጣጥፉ “Apropos of Lady Chatterley’s Lover” ላይ ይኼንን ኹኔታ አሳምሮ ገልፆታል፡፡ ሮማንስ  ውስጥ ያሉ ሰዎች “ምን ዓይነት ስሜት ሊሰማቸው እንደሚገባ ያውቁታል፣ ስለዚህም ያንን ስሜት ያድኑታል ግን እውነተኛ ስሜት አይደለም” ቃል በቃል ማስታወስ ባለመቻሌ ይቅርታ መጠየቅ ይገባኛል፡፡)
“ፍቅር ሁሉንም ነገር ይቆጣጠራል እንባላለን” ይላል- ከላይ የጠቀስኩት ጸሐፊ ሱሊይቫን ደግሞ፡፡ ነገር ግን በቫለንታይን ቀን የሚከበረው ፍቅር ምንም የሚቆጣጠረው ነገር የለም! ሩሶ የተባለው ተምኔታዊ ፈላስፋ በከበርቴው መደብ ጠባይ እና ነገረ ሥራ በመማረሩ ሰዎች ለእውነት፣ ለክብር እና ለስልጣን ያላቸውን ጥልቅ ስሜት በሌላ መተካት እንዳለበት አመነ፡፡ እና ወጣቶች በርስ በርስ ጥማት መንደዳቸው አስፈላጊ ነው ሲል ሰበከ፡፡ (በምዕራባውያን ባህል መዋደድ ለጋብቻ መሰረት መሆኑ ይለመድ የያዘው ከ19ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶም የፍቺ ቁጥር ጨመረ እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡) ሮማንስ  ለዘመኑ ወጣቶች የሚሰጠው ብዙ ጥቅም አለ፡፡
ኢጓችንን ደባብሶ ይንከባከብልናል፡፡ በራሳችን ዙሪያ መተብተባችን ያለቅጥ እየጦዘ ነው የመጣው። ሮማንስ  ይህንን ራስ ወዳድነታችንን ያረካልናል። እንደ ወትሮው ልጅ መውለድ ዋነኛ ዓላማው ተደርጎ መታየቱ፣የቀረውን ወሲብ ልዩ ትርጓሜ የያዘ እንዲመስል ያደርገዋል፡፡ እናም ደግሞ ከመራር የህይወት ጥያቄዎች (ምን እንመን? ምንድን ነን? ወዘተ) ይገላግለናል፡፡ ይሸሽገናል፡፡
ይህ የኑሮ ፈሊጥ አሁን የእኛም ሆኗል፡፡ ችግር መሆን የሚጀምረው ግን ትክክለኛ ዋጋውን ያለአግባብ ለጥጠን የሌለውን ግዝፈት ከሰጠነው ብቻ ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ

የእነ ሶፊ መንገድ…
ከሴተኛ አዳሪነት ወደ ፋርማሲስትነት

“… በአጠቃላይ ታሪኩ ይሄው ነው፡፡ ሶፊያ በድጋሚ እንኳን ደስ አለሽ!!” በማለት ንግግሩን ቋጨ - ኢሻይ ሃዳስ፡፡ ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላው የዩኒቨርሲቲው አዳራሽ ከዳር እስከ ዳር በጭብጨባ ተናወጠ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎች፣ የዕለቱ ተመራቂዎች፣ የተመራቂዎች ቤተሰቦች… ሁሉም በደስታ እንባ ተራጩ፡፡  ሁሉም የየራሱን ደስታ ትቶ፣ በሁለቱ ደስታ ፈነደቀ - በኢትዮጵያዊቷ ተመራቂ በሶፊያና በእስራኤላዊው እንግዳዋ በኢሻይ ሃዳስ፡፡
ሶፊያ ብቻዋን ናት፡፡
የኔ የምትለው ወዳጅ ዘመድ ወይም  ጓደኛ ያልነበራት ባይተዋር! ብቻዋን ነው፣ ባልጠና ጉልበት ከኑሮ ጋር ትግል የጀመረችው፡፡ ስትወድቅ ስትነሳ ከጎኗ ማንም አልነበረም፡፡ ወድቃ ከምትቆዝምበት ድንገት ደርሶ ካቃናት፣ ቀና አድርጎ ካቆማት፣ መንገዷን ከጠረገላት፣ ደግፎ ከዚህ ካደረሳት ካልተወለዳት ዘመዷ በቀር እሷ ሰው አልነበራትም፡፡
አሁን ሶፊያ ብቻዋን አይደለችም፡፡ እንደሌሎች ተመራቂ ጓደኞቿ በደስታዋ ቀን ከጎኗ የሚቆም፣ “እንኳን ደስ አለሽ!” ብሎ እቅፍ አበባ የሚሰጣት፣ እቅፍ አድርጓት ፎቶግራፍ የሚነሳ፣ የራሷ ሰው መጥቶላታል - በእቅፏ ውስጥ ሆኖ ከእንባዋ በስተጀርባ ሲፍለቀለቅ የምታየው እስራኤላዊው ኢሻይ ሃዳስ፡፡
ይህ ሰው ከአመታት በኋላ ጊዜ ቆጥሮ፣ በዚህች ልዩ ዕለት ከጎኗ እንደሚገኝ የምታውቀው ነገር አልነበረም፡፡ እሷ የምታውቀው ሰውዬው ከአመታት በፊት የህይወቷን ጉዞ ወደሌላ አቅጣጫ መርቶ ለዚህች ልዩ ዕለት እንዳበቃት ብቻ ነው፡፡ ይሄን ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ይሄ ምንጊዜም ከልቧ የማይጠፋ እውነት ነው - በጊዜ የማይሻር፡፡
በ1996 ዓ.ም… ከወርሃ ሃምሌ የመጨረሻዎቹ ቀናት በአንደኛው…
ከአዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ በ736 ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኝ አንዲት የመሸባት የገጠር ከተማ… ጨለማው ውስጥ ተኮራምታ የምታንጎላጅ መንደር… መንደሯ ውስጥ አንዲት የከተማዋ ብቸኛ ቡና ቤት… ቡና ቤቷ ውስጥ አንዲት ጉብል - ጥግ ላይ ተቀምጣ የምትቆዝም፡፡
እጅ እግርን የሚያደነዝዝ ቆፈን፣ ውስጥ ድረስ ዘልቆ ከሚያንሰፈስፍ ብቸኝነት ጋር ተባብሮ የሚያሰቃያት የ19 አመቷ ኮረዳ፣ ከጠባቧ ቡና ቤት አንድ ጥግ ላይ ተኮራምታ ቁጭ እንዳለች ትተክዛለች፡፡ አንድ ሁለት ማለት ያሰኘው የመሸበት ጠጪ እስኪመጣ፣ በራሷ ሃሳብ ተውጣ ትቆዝማለች፡፡ ተስተናጋጅ ብቅ እስኪል፣ የህይወቷን ጣጣ ታወጣ ታወርዳለች፡፡
ወላጆቿን የነጠቃት ክፉ ሞት፣ ተራውን ጠብቆ መጥቶ እሷንም እስኪገላግላት ለቡና ቤቷ ደንበኞች መጠጥ እያመላለሰች ትጠብቃለች፡፡ ደጋፊ ዘመድ አጥታ ባቋረጠችው ትምህርት ምትክ፣ የመከራን ሀሁ ስትቆጥር ውላ ማምሸት ከጀመረች ሁለት ሳምንታት አልፈዋታል፡፡ የመሰደብ… የመጎንተል… የመዋረድ… የመናቅ…. እንዲህና እንዲያ የመሆን የማይገፉ አስቀያሚ ሁለት ሳምንታት!
ሶስተኛው ሳምንት ከመምጣቱ በፊት…
ከአስጠሊታዎቹ ምሽቶች ባንደኛዋ፣ የመሸበት ተስተናጋጅ ወደ ቡና ቤቷ ጎራ አለ፡፡ ፈረንጅ ነው - ከጥቁሩ ጨለማ ውስጥ ድንገት ብቅ ያለ የነጭ ጥቁር እንግዳ፡፡
“ወይ ጣጣ!... መቼም እንቅልፍ የሚነሳ አንዳንድ ሰው አይታጣ!... ይሄ ደሞ ምን ያለው ነው፣ ሌት አጋምሶ የሚመጣ?!” ስትል በውስጧ እያጉተመተመች ከተቀመጠችበት ተነሳች፡፡ ወደተቀመጠበት በማምራትም ጎንበስ ብላ ምን እንደሚፈልግ በትህትና ጠየቀችው፡፡ እርግጥ ለወጉ ብላ ነው እንጂ፣ ምን እንደሚፈልግ አጥታው አይደለም፡፡ ቢራ ወይም ወሲብ፣ ከሁለቱ አንዱ ነው ወንዶችን ከመሸ ወዲህ የሚያመጣቸው፡፡
“ምን ልታዘዝ?” በትህትና ጠየቀች አስተናጋጇ፡፡
የ58 አመቱ እስራኤላዊ የማስታወቂያ ፕሮዲዩሰር ኢሻይ ሃዳስ፣ ከፊቱ ላለችው አስተናጋጅ መልስ አልሰጣትም፡፡ ለአርኪዎሎጂ ጥናት ከአገሩ የወጣው ሃዳስ፣ እንደ ድንገት ነው እዚህ የተገኘው። ስለመሸበትና ጉዞውን መቀጠል ስለማይችል ነው፣ እዚህች ትንሽዬ የገጠር ከተማ ለማደር ወስኖ ድንኳን የጣለው፡፡ ከወዲያ ወዲህ እያለ ሲናፈስ ድንገት አይኑ ውስጥ ወደገባችው ወደዚህች አንድ ላገሯ ቡና ቤት ጎራ ያለው በአጋጣሚ ነው፡፡ እንዲሁ ሁኔታውን ለማየት፡፡
“ምን ልታዘዝ ?” ስትል ግራ በመጋባት ደግማ ጠየቀች አስተናጋጇ፡፡ የፈረንጁ ሁኔታ አላማራትም። ወሲብ ሊሸምት ጎራ ያለ አይናፋር ፈረንጅ ሳይሆን አይቀርም ስትል አሰበች፡፡ ጥቂት ቆይታ ደግሞ፣ ችግሩ የቋንቋ ሊሆን እንደሚችል ጠረጠረች - ያለመግባባት፡፡  
እሷ እንደጠረጠረችው ችግሩ የቋንቋ አልነበረም። ኢሻይ ሃዳስ ከፊቱ የቆመችውን አስተናጋጅ በድምጽ ሳይሆን በገጽ መረዳት የቻለ ሰው ነው፡፡ አፍ አውጥታ ከጠየቀችው አልፎ፣ ከውስጧ የደበቀችውን ሰምቶ መረዳት ችሏል፡፡ ፊቷ ላይ ምሬት አንብቧል፡፡ መላ ሁኔታዋ ላይ ደስታ ማጣት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ባይተዋርነት ተመልክቷል፡፡ ይህቺ ከፊትለፊቱ የቆመች ሴት፣ እንደነዚያ ባንኮኒው ስር ቁጭ ብለው ሲያሽካኩ እንደሚያያቸው ሁለት የስራ ባልደረቦቿ አይደለችም፡፡ ቢያንስ እንደነሱ የውሸትም ቢሆን እየሳቀች ኑሮን ለማሸነፍ የሚሆን አቅም የላትም፡፡
“መላ ነገሯን ሳየው፣ ያለቦታዋ ያለች ሴት እንደሆነች ተረዳሁ፡፡ ቡና ቤቷ ውስጥ የነበሩት ሌሎች ሁለት አስተናጋጆች፣ ዕጣ ፈንታቸውን በጸጋ የተቀበሉ ይመስላሉ፡፡ እሷ ላይ ግን የሆነ ነገር አነበብኩ፡፡ አለ አይደል የሆነ የተደበቀ ነገር…” ይላል ኢይሻ ሃዳስ በወቅቱ ስለተከሰተው ነገር ሲያስታውስ፡፡ እግር ጥሎት በምሽት ወደ ቡና ቤቷ ጎራ ያለው ሃዳስ፣  መጠጡን ችላ ብሎ ቀልቡን ወደዚህች ልጅ እግር አስተናጋጅ ያደረገውም ሆነ፣ ጥቂት አግባብቷት ካሜራውን መዝዞ ቃለመጠይቅ ያደረገላት፣ ይሄን የተደበቀ ነገር ፍለጋ ነው፡፡
ሲቃ እየተናነቃት ታሪኳን በሙሉ ዘክዝካ ነገረችው፡፡ ነግራው ስትጨርስ አይኖቿ እንባ እንዳቀረሩ አቀርቅራ ዝም አለች፡፡
“እኔ እምልሽ ሶፊያ… የሆነ ገንዘብ ብታገኚ ምን መስራት ነው የምትፈልጊው?” ሲል ድንገተኛ ጥያቄ ሰነዘረላት ሃዳስ፡፡
“መማር!... ተምሮ ነርስ መሆን!!” ለእንዲህ ያለ ድንገተኛ ጥያቄ ቆጥባ ያስቀመጠችው መልስ ያላት ይመስል ፈጥና መለሰች፡፡
እስራኤላዊው እንግዳ ለራሱ ቃል ገባ፡፡ ከዚህ ሲኦል የሆነ ኑሮ ሊያወጣትና ወደ ህልሟ ደግፎ ሊያደርሳት ወሰነ፡፡ ያቋረጠችውን ትምህርት አጠናቅቃ ኮሌጅ እስክትገባ ድረስ ወርሃዊ ወጪዋን እንደሚሸፍንላት ነገራት፡፡ ይህን የሚያደርገው ግን ከዚህ አሰቃቂ የቡና ቤት ስራ በአፋጣኝ ከወጣች ብቻ መሆኑን አስረዳት፡፡
ሶፊያ ድንገት እግር ጥሎት የመጣን አንድ የማታውቀው ሰው አምና፣ የአስተናጋጅነት ስራዋን ለመልቀቅ ከብዷት ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን፣ ከዚህ ስራ የምታጣው ነገር እንደማይኖር ስለገባት በሃሳቡ ተስማማች፡፡ ስራውን እንደምታቆም፣ ትምህርቷን እንደምትቀጥል በአንዲት ቁራጭ ወረቀት ላይ አስፈረማት፡፡
በነጋታው ጧት…
እስራኤላዊው መንገደኛ ልብሶቿን በአሮጌ ፌስታል የሸከፈችውን ሶፊያን አሳፍሮ በ300 ኪሎ ሜትሮች ርቃ ወደምትገኝ ሰፋ ያለች ከተማ መኪናውን ሲያሽከረክር ታየ፡፡
እዚያች ከተማ ደርሰው ነገሮችን ካመቻቸላት በኋላም፣ ለጊዜው ለአንዳንድ ወጪ መሸፈኛ የሚሆናት 300 ዶላር ሰጥቷት፣ በየወሩ ገንዘብ እንደሚልክላት ቃል ገብቶላት አድራሻውን ሰጥቷት ተሰናበታት፡፡ ቃል አክባሪ ይሁን ቀልማዳ እርግጠኛ ያልሆነችበትን የሰው አገር ሰው ከልቧ አመስግናውና ቸር እንዲያደርሰው ተመኝታለት ተለየችው፡፡
ሃዳስ እውነቱን ነበር፡፡
 የገባውን ቃል የሚያከብር ትልቅ ሰው ነው፡፡ ሃዳስ ለቃሉ የሚታመን እውነተኛ ፈረንጅ ነው፡፡ ሶፊያን ተሰናብቶ ወደ እስራኤል ከተመለሰ በኋላም፣ ስለ ሶፊያ ማሰቡን አላቆመም፡፡ የገባላትን ቃል ከመፈጸም ወደ ኋላ አላለም፡፡ ወር ከወር እየጠበቀ ለሶፊያ አንድ መቶ ዶላር መላኩን ቀጠለ፡፡ ሶፊያም ትምህርቷን ቀጠለች፡፡
ሶፊያና ሃዳስ ቢራራቁም አልተለያዩም፡፡ በየጊዜው ይጻጻፋሉ፡፡ ኢ-ሜይል ይደራረጋሉ። ትምህርቷን በጥሩ ሁኔታ እየተማረች እንደሆነ ትነግረዋለች፡፡ በደስታ ይፈነጥዛል፡፡ በርቺ ይላታል።
በዚህ ሁኔታ ዘጠኝ አመታት አለፉ…
ስለ ሶፊያ ያጫወታቸው የሃዳስ ጓደኞች ነገሩ አልጣማቸውም፡፡  “ይሄን ያህል አመት ምን የሚሉት ትምህርት ነው?  ወዳጄ  የምትላት ሴት ትምህርት ማለቂያ ያለው አይመስልም! ዝም ብለህ ነው ገንዘብህን የምትገፈግፈው! ” በማለት እየተጃጃለ መሆኑን ሊነግሩት ሞከሩ፡፡
እሱ ግን ለእንዲህ ያለው ወሬ ጆሮ መስጠት አልፈለገም፡፡ እርግጥ ዘጠኝ አመት ቀላል ጊዜ አይደለም፡፡ ሶፊያ ትምህርቷን ለመጨረስ ረጅም ጊዜ ፈጅቶባታል፡፡ እሱ ግን  በእርግጥም ትምህርቷን እየተከታተለች እንደሆነ የሚያረጋግጥበት መንገድ አልነበረውም፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ ሃዳስ በወሬና በጥርጣሬ ተነስቶ ቃሉን ማጠፍ  አልፈለገም፡፡ ገንዘብ መላኩንም አላቋረጠም፡፡
የሆነ ቀን…
ሃዳስ ከሶፊያ የተላከ ኢ-ሜይል ደረሰው፡፡
“እንኳን ደስ አለህ ሃዳስ!... በቅርቡ በፋርማሲ በዲግሪ እመረቃለሁ!...” ይላል መልዕክቱ፡፡ ሃዳስ መልዕክቱን አንብቦ እንደጨረሰ በደስታ ፈነደቀ። ከአቅሙ በላይ የሆነ፣ ሊሸከመው አቅም ያጣለት፣ ሊቋቋመው የቸገረው ደስታ ውስጡን አጥለቀለቀው።
ሃዳስ ከኢትዮጵያ ለተላከለት የሶፊያ የኢ-ሜይል መልዕክት ምላሽ አልላከም - ራሱ ወደ ሶፊያ መጣ እንጂ!
የምረቃዋ እለት…
“… በአጠቃላይ ታሪኩ ይሄው ነው፡፡ ሶፊያ በድጋሚ እንኳን ደስ አለሽ!!” በማለት ንግግሩን ቋጨ - ኢሻይ ሃዳስ፡፡
ይሄን ተከትሎ… ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላው የዩኒቨርሲቲው አዳራሽ ከዳር እስከ ዳር በጭብጨባ ተናወጠ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎች፣ የዕለቱ ተመራቂዎች፣ የተመራቂዎች ቤተሰቦች… ሁሉም በደስታ እንባ ተራጩ፡፡  ሁሉም በየራሱ መደሰቱን ትቶ፣ በሁለቱ ደስታ ፈነደቀ - በኢትዮጵያዊቷ ተመራቂ በሶፊያና በእስራኤላዊው እንግዳዋ በኢሻይ ሃዳስ፡፡
ከምረቃው በኋላ…
ሶፊያ ለመንፈስ አባቷ ለሃዳስ ሌላ የምስራች አበሰረችው - “የልጅ እናት ሆኛለሁ!”
ሃዳስ የሰማውን ለማመን ተቸግሮ እያለ፣ የሶስት አመት ድንቡሽቡሽ ህጻን ድክድክ እያለ ወደ እሱ ሲመጣ ተመለከተ፡፡ የሶፊያ ልጅ ነው፡፡
“ልጅ መውለዴን ለምን እንዳልነገርኩህ ታውቃለህ ሃዳስ?… ያኔ ቡና ቤቷ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንገናኝ ፣ ትምህርቴን ሳልጨርስ እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ እንደማልገባ ቃል ገብቼልህ አልነበር?!... ቦይ ፍሬንድ መያዜንና ማርገዜን ብነግርህ ቃል አባይ ናት ብለህ እንዳትከፋ ሰግቼ ነው የደበቅሁህ!... ከቦይፍሬንዴ ካረገዝኩ በኋላ ትዳር እንድንመሰርት ጥያቄ አቅርቦልኝ ነበር፡፡ እኔ ግን እምቢ አልኩት!... ምክንያቱም ትምህርቴን ሳልጨርስ ትዳር አልይዝም ብዬ ቃል ገብቼልሃለሁ!... አልተቀየምከኝም አይደል ሃዳስ?” አለች ሶፊያ ልጇን አቅፋ ወደ ሃዳስ እየተጠጋች - ፈገግ እንዳለች፡፡
ሃዳስ እንዳልተቀየማት በፈገግታ ፀዳል የፈካው ፊቱ ነገራት፡፡
“በፍጹም አልቀየማትም!... እሷ’ኮ… በሰው ልጅ ላይ ያለኝን እምነት እንዳላጣ  ያደረገችኝ ትልቅ ሰው ናት!...” ብሏል እስራኤላዊው ኢሻይ ሃዳስ፡፡

Published in ህብረተሰብ

          “ደራሲ፣ አከፋፋይና አዟሪ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባለፈው ቅዳሜ በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መፃሕፍት የተካሄደው ውይይት ለኢትዮ ደራስያን ማህበር አዲሱ አመራር የመጀመሪያው የውይይት መድረክ ነበር፡፡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተጋበዙበት በዚህ የውይይት መድረክ፤ የመፃሕፍት ስርጭትን ተግዳሮት በሚመለከት ለውይይት መነሻ የሚሆን ሐሳብ ያቀረቡት ደራሲና ጋዜጠኛ ደሳለኝ ሥዩም ናቸው፡፡
በቀድሞ የአገራችን የድርሰት ታሪክ፤ ደራሲያን ሥማቸው በመጽሐፋቸው ላይ እንዳይወጣ እስከ ማድረግ የሚደርስ ትህትና እንደነበራቸውና ለአእምሮ ጭማቂ ውጤት ዋጋ የመጠየቅ ባህል እንዳልነበረ ያስታወሰው ደሳለኝ ስዩም፤ በወቅቱ በቀናነት የተፈፀመ ቢሆንም፤ ቆይቶ ግን ያስከተለው ጉዳት ቀላል አይደለም ብሏል፡፡ አንባቢያን የመጽሐፍን ዋጋ ዝቅ አድርገው እንዲገምቱ ያደረጋቸው አንድም በዚህ ምክንያት ነው ሲል አስረድቷል፡፡
ሕብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ተቋማት ወንበርና ጠረጴዛ ለመግዛት በሚጨነቁት መጠን መፃሕፍት ለመግዛት የማይጓጉበት ምክንያት፤ ቀበሌዎች ለወጣቶች መዝናኛ ሲያደራጁ መፃሕፍት አሰባስበው ወደ ማዕከሎቹ ለማስገባት ዝቅ ያለ ትኩረት የሚሰጡት…የቆየው ልማድ በፈጠረው ተጽዕኖ መሆኑንም ደራሲና ጋዜጠኛ ደሳለኝ አመልክቷል፡፡
ይህ ችግር ባልተቀረፈበት፣ የአገሪቱ የሕትመት ኢንዱስትሪም በሚገባው መጠን ባላደገበት፣ የሚታተሙት መፃሕፍት በብዛትም ሆነ በጥራት በማይቀርቡበት ሁኔታ ደራሲው ያስቀመጠውን ዋጋ እየፋቁ አዲስ ዋጋ መለጠፍ የዘርፉ ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ ተገልጿል፡፡  መሆኑን ከማነጋገር አልፎ የዕለቱ የውይይት መድረክ እንዲሰናዳ ምክንያት መሆኑን ዳሰሳ አቅራቢው ካመለከተ በኋላ “ማሳያዎቼ” ያላቸውን መረጃዎች አቀረበ፡፡
የ32 ብሩ መጽሐፍ 3 ቁጥርን ወደ 8 በመለወጥ 82 ብር እንደተባለ፤ 18.70 የተቀመጠለትን ዋጋ ከነጥብ በፊት ያለውን ቁጥር በማጥፋት 70 ብር ለመሸጥ እንደተሞከረ፤ የ25 ብሩ መጽሐፍ ላይ ከፊቱ ዜሮ በመጨመር በ250 ብር ሲሸጥ ማየቱን ደሳለኝ ስዩም ገልጿል፡፡ ይህንን አሰራር ተቃውመው በጋዜጣ የፃፉና በሬዲዮ የተናገሩ ደራሲያንን ሥራ ላለማከፋፈልና ላለማዞር ተስማምተው የተማማሉ ነጋዴዎች እንዳሉም በዳሰሳ ጽሑፍ አቅራቢው ተመልክቷል፡፡
ዋጋቸው ለመፋቅ ምቹ ያልሆኑ መፃሕፍትን ለመያዝ አዟሪዎች ፍላጐት እንደሌላቸው፤ በዚህም ምክንያት ደራሲያን የመጽሐፍ ዋጋ ሲወስኑ ለመፋቅ ምቹ እንዲያደርጉት በአከፋፋዮች እንደሚነገራቸው  ዋጋውን ብቻ ሳይሆን የመጽሐፉ ሽፋን መያዝ ስላለበት ምስልና ቀለም ወሳኞቹ እነሱ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፆ ዳሰሳውን ካጠናቀቀ በኋላ የተለያዩ ሃሳቦች ተንሸራሸሩ፡፡
በአገራችን ብዙ ነገር ሲጨምር የመፃሕፍት ዋጋ ባለበት ነው የቆመው፡፡ 40.90 ዋጋ የተቀመጠለት መጽሐፍ፤ 40ው ተፍቆ በ90 ብር የሚገዛ ካለ የገዢ አቅም እንዳለ ነው የሚያመለክተው፡፡ ሌሎች ከሚወስኑልን እኛ ለምን ቀድመን አናስተካክልም?
በእኛ አገር ግብይት የመከራከር ባህል ስላለ፣ መጽሐፍ አዟሪዎችን ዋጋ ፍቀው አዲስ እንዲለጥፉ ያደረጋቸው ይህ ልማድ ነው፡፡
የቀድሞ ዘመን መፃሕፍት ከገበያው በመጥፋታቸው ምክንያት ከመጀመሪያ ዋጋቸው በብዙ እጥፍ የጨመረ ዋጋ እንዲለጠፍባቸውና እንዲጠራላቸው ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በገበያው የሚፈለጉ መፃሕፍት አሳትሞ ለአንባቢያን የሚያደርስበትን ዘዴ ቢፈልግ…
ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው፤ ደራሲያን በሥራቸው እንደማይጠቀሙት ሁሉ አከፋፋዮችም አዟሪዎችም ብዙ ችግር አለባቸው፡፡ ለትንሽ “የአርከበ ሱቅ” በወር ከ3ሺህ ብር በላይ ኪራይ ከፍለው መጽሐፍ ነግደው ለመኖር የሚጥሩ አሉ፡፡ መጽሐፍ አዟሪዎችም ከሕግና ደንብ አስከባሪዎች ጋር እየተሳደዱ ነው የሚሰሩት፡፡
አሁን ለተፈጠረው ችግር ብቸኛ ተጠያቂ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ በዘርፉ የተፈጠረውን ተግዳሮት እያዩ፤ አዟሪዎች ለመፋቅ የሚመቻቸውን ዋጋ በመጽሐፋቸው ላይ የሚያሰፍሩ ደራሲያን አሉ። መጽሐፉ ላይ 40 ብር ከ95 ሣንቲም የፃፈ ደራሲ አስቦበት ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል፡፡
አንዱ ከተጐዳ ችግሩ ሌሎች ዘንድም መድረሱ አይቀርም፡፡ በተለይ የደራሲያንን ተሰጥኦ የሚጐዳ ነገር ለመጽሐፍ አከፋፋዮችና አዟሪዎች ብቻ ሳይሆን የሕብረተሰብን ንቃተ ህሊና የሚያንጽ ምንጭም ነው የሚያደርቀው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ትልቅ ችግር ለመቅረፍ የደራሲያን፣ የአሳታሚዎች፣ የአከፋፋዮችና የአዟሪዎች ጠንካራ ማህበራት መመስረትን ይጠይቃል፡፡ ይሄን ካደረጋችሁ አሁን እየተነገረ ያለው ችግር ብቻ ሳይሆን የወረቀት ዋጋ ውድነት ማስቀነስን ጨምሮ መንግሥት ባወጣቸውና በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ላይ ጫና ማሳደር ይቻላችኋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችና አስተያየት ከተንሸራሸረ በኋላ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ፤ ችግሩን የሚመሩት ማህበር ብቻውን መቅረፍ እንደማይችል አመልክተው ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ እንዲዋቀር ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ ተሰብሳቢዎችም በሀሳቡ ስለተስማሙ፣ ከመፃሕፍት ጋር በተያያዙ ከሚሰሩ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከዩኒቨርስቲ፣ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከፖሊስ፣ ከመከላከያ…የተውጣጡ ተወካዮችን በመምረጥ ጉባኤው ሲጠናቀቅ ኮሚቴው የሚደርስበትን ውጤት፤  ማህበሩ እንደሚያሳውቅ ቃል ገብቶ ስብሰባው ተጠናቀቀ፡፡
የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ያሰናዳው ሌላው መድረክ፤ ባለፈው ማክሰኞ ጥር  27 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የተከናወነ ሲሆን፤ ፕሮግራሙም ደራሲ መስፍን ሃብተማርያምን የሚዘክርና በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ላበረከተው አስተጽዋኦ ዕውቅና ያለመ ለመስጠት ነበር፡፡
አዲስ ምርጫ ተካሂዶ የአመራር ኃላፊነቱን ከተረከበ 4 ወራት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር፤ ለ2006 ዓ.ም ተግባራዊ ሊያደርግ ካቀዳቸው ፕሮግራሞች መካከል በሕይወት ያሉና የሌሉ ደራስያንን መዘክርና ዕውቅና መስጠት ነው ያሉት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ፤ ቀዳሚውን መድረክ ለደራሲ መስፍን ሀብተማርያም በመስጠት መጀመራቸውንና በዚህ ዓመት በተመሳሳይ መልኩ ተግባራዊ የሚሆኑ ሦስት መድረኮች ለማሰናዳት መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ፀሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በበኩላቸው፤ “በደቦ ያዘጋጀነው ነው” ያሉትን የደራሲ መስፍን ሃብተማርያም የሕይወትና የሥራ ታሪክ አቅርበዋል፡፡ “የአንድ ደራሲ ታሪክ የአንድ አገርና ሕዝብ ታሪክ ነው” ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ “ሁለገቡ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ መስፍን ሀብተማርያም ከሕዝብ ሳይነጠል፣ ወደ ኋላም ቀርቶ ሕዝብ ሳይጐትተው፣ ከፊት እየቀደመ ሕዝብን ያስተማረ ነው” በማለት አድንቀውታል፡፡
“ብሔራዊ ጀግኖች ይኑሩን” በሚል ርዕስ ቀጣዩን ንግግር ያቀረቡት መጋቢት ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ ሲሆኑ “ከዚህ ቀደሙ ልምዳችን እንደታየው የሞተን የምናመሰግነው የቆመውን ለማበሳጨት ነው” በማለት የመደናነቅና የመከባበር ችግር እንዳለብን በቀልድ እያዋዙ ገልፀዋል፡፡
 የጋራ ዛፍ፣ ሜዳ፣ ወንዝ…እያለን በጋራ የምናከብረው ብሔራዊ ጀግና እንዴት እናጣለን? ሲሉ የጠየቁት መጋቢ ሃዲስ፤ ገበሬዎቿን የምትሸልም አገር ለሰው ልጅ ዕውቀት መዳበር ትልቁን ሚና የሚጫወተውን ደራሲ መዘንጋት ተገቢ ነው ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ደራሲ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ የሰውን ልጅ ብልሹና አውሬ ፀባይ ለማረቅ የሚጥር ነው ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ “አእምሮ የሰው ልጅ መመሪያ የሚመነጭበት ማዕከላዊ እዝ ነው፤ በዚህም ምክንያት ነው እግዚአብሔር አእምሮን ዙሪያውን በአጥንት በተሸፈነ ቦታ ያኖረው፡፡ ደራሲያን ደግሞ ባለ ልዩ አእምሮ ናቸው” ብለዋል፡፡
ዮሐንስ አፈወርቅ የሚባሉ የቅኔ ሊቅን ጠቅሰው “የቀድሞውን እያመሰገንን በሄድን ቁጥር ለመጪውም ይተርፈናል” ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ አፄ ቴዎድሮስን፣ ዮሐንስን፣ ምኒልክን አገራዊ ማድረግ ትተን የመንደር ጀግኖች ለማድረግ መትጋታችን ትክክል አይደለም ካሉ በኋላ ቀዳሚው ኋለኛውን የሚያለሰልስ፣ የሚሞርድ ብርጭቆ ወረቀት መሆኑን አንዘንጋ በማለት አሳርገዋል፡፡
ዕውቅናና አክብሮት ለመስጠት በኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር በተመረጠው በደራሲ መስፍን ሀብተማርያም ሥራዎች ላይ ሁለት ወጣት ምሁራን ጥናታዊ ሥራቻቸውን ያቀረቡበት ቀጣዩ ፕሮግራም ነበር፡፡ ባዩልኝ አያሌው ባቀረበው ጥንታዊ ፅሁፍ “መስፍን ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ሐያሲ፣ የዘመናዊ ወግ ፀሐፊ፣ ጋዜጠኛ” መሆኑን ገልፆ “ወግ ምንድነው? ባሕሪያቱስ?” በሚል  በመስፍን ሀብተማርያም ሥራዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶችን አስቃኝቷል፡፡
የፒኤችዲ ተማሪው ገዛኸኝ ፀጋው በበኩሉ፤ “በመምህርነት ሙያ እንዳቅሜ ከገጠር እስከ ከተማ እየተዟዟርኩ ሳስተምር ካስተዋልኩት ነገር አንዱ መስፍን ሀብተማርያም ወግ መፃፍ የሚችሉ ብዙ የልጅ ልጆችን ማፍራት መቻሉን ነው” ካለ በኋላ፤ ከ1951 -1960 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይቀርቡ የነበሩ “የኮሌጅ ቀን ግጥሞች” እና ደራሲ መስፍን ሃብተማርያም የነበራቸውን ግንኙነት የሚያስቃኝ ጥናቱን አቅርቧል፡፡ “በዘመኑ የቀረቡት የመስፍን ግጥሞች ወጣቶች በብዕር ያደርጉት የነበረውን ትግል አቅጣጫ ወደ ሌላ የመራ ይመስለኛል” በማለትም አጠቃሏል፡፡
ቀጣዩ ንግግር አቅራቢ የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ሲሆኑ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ጥቅስ በማስቀደም ነበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፡፡ “መጀመር ቀላል ሲሆን መጨረስ ከባድ ነው፤ ሊያስመሰግን የሚገባው መጨረስ ነው እንደተባለው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ዛሬ የጀመረው ሳይሆን ይበልጥ የሚያጓጓው፤ መድረሻና ዘለቄታው ነው፡፡ ይህ ጅማሬ ተቋማዊ ሆኖ በሚቀጥለውስ ማን ይሆን የሚሸለመውና ዕውቅና የሚሰጠው? የሚል ጉጉት በሕዝብ ዘንድ ለመፍጠር በትጋት መስራት እንዳለባችሁ አደራ እላለሁ፡፡”
ዕውቅናና ሽልማት ከተሰጠው በኋላ ደራሲ መስፍን ሃብተማርያም በበኩሉ፤ “በአሁኑ ጊዜ በሕመም ምክንያት የተጐዳሁ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት መድረክ አዘጋጅታችሁ ስታበረታቱኝ፣ መልካም ምኞት ስትገልፁልኝ፣ ቅንነታችሁን ስላሳያችሁን ተበረታትቻለሁ” በማለት አመሰግኗል።
የደራሲ መስፍን ሀብተማርያምን ያልታተሙ ሥራዎች ለአንባቢያን ለማድረስ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የሚችለውን ከማድረግ ወደኋላ እንደማይል ቃል በተሰጠበት በዕለቱ ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛና ገጣሚ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን የ1000 ብር ስጦታ ለደራሲ መስፍን ሀብተማርያም አበርክቷል፡፡ የመድረክ ዝግጅቱ በሙዚቃና ወጣቶች ባቀረቧቸው የተለያዩ ግጥሞች የደመቀ ነበር፡፡   



Published in ህብረተሰብ

           ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ነበር ወይ? ብዬ በመጠየቅ ያቀረብሁተን ጽሑፍ ለመቃወም የታሰበበት ጽሑፍ ባለፈው ሳምንት በደረጃ ኅብስቱ ቀርቧል፡፡ ጸሐፊው በእርግጥ በስም ተቅሰው እኔን እንደሚመለከት ባይገልፁልኝም በቅርቡ የጻፍኩት እኔው ብቻ በመሆኔ የአቶ ደረጄም ጽሑፍ ይህንኑ ጽሑፌን እንደሚመለከት ለመገመት አያዳግትም፡፡
ደረጀ ኅብስቱ ፮ ድረስ የተቆጠሩ መከራከሪያ ሐሳቦችን አቅርበዋል… ነገር ግን እንዳሉ ለዚህ ባበቃቸው የእኔ ጽሑፍ ላይ ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ መኖሩን ለመጠየቅ ያበቃኝን ሐሳብ በቀጥታ ያገኟቸው አልመሰለኝም… ስድስቱም ነጥቦቻቸው ዘርዓያዕቆብ አበሻ አይደለም፤ ፈረንጅ (አውሮፓዊ፣ ሮማዊ) እንጂ” ለሚሉ ሰዎች የቀረቡ መሟገቻ ሐሳቦች ናቸው፤ እነዚያውም አቅም የሌላቸው፡፡ እኔ ደግ ይህን አላልኩም እስኪ የደረጄን ፮ ነጥቦች እንያቸው፡፡
፩/ ዘርዓ ያዕቆብ ተብሎ በተጻፈው መጽሐፍ፣ ይኼው ገጸ ባህርይ “ዳዊት ለ፫ ወር፣ ቅኔ ለ፬ ዓመት፣ መጽሐፍ ለ፲ዓመት” ጠቅላላ ለ፲፬ ዓመት በአብነት ትምሕርት ከውሻና ከችግጋር ጋር እየታገለ … መከራውን እየታገሰ የሚማረው ኢትዮጵያዊ ካልሆነ በቀር ሌላ ማንም እንዳልሆነ ታሪካችን ይመሰክራል” ይኼን መከራ ታግሶ መማር የሚችል “አውሮፓዊ ከተገኘ እሰየው ነው፡፡”
፪/ ዘሩን ከካህናት፣ ከደኃ ወገን የሚቆጥር ሮማዊ ይገኛል ወይ? ከደኃ ቤተሰብ መወለዱም ለኢትዮጵያዊ እንጂ ለአውሮፓዊ አይሆንም…
፫/ “የሐሳቡን አደረጃጀትና አቀራረብ ከአውሮፓዊያን በማመሳሰላቸው ነው” ዘርዓ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚሉት፤
፬/ ዘርዓ ያዕቆብ አውሮፓዊ ቢሆን ኖሮ ሸሽቱ ወደ ዋሻ ሳይሆን ወደ ቀይ ባህር በኾነ ነበር፡፡  
፭/ ዳዊቱን አንግቦ መሰደዱ ራሱ ፍጹም ኢትዮጵያዊነቱን ይመሰክራል፡፡
፮/ በመጽሐፉ እንደቀረበው ከሽሽት በኋላ ማለትም የአፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት አክትሞ የአፄ ፋሲል ዘመን ላይ የተጻፈ መምሰሉንም በመያዝ፣ በዚህ በአፄ ፋሲል ዘመን ደግም ፈረንጅ ኹሉ ተባርሮ ነበር፡፡ “ዘርዓ ያዕቆብ ፈረንጅ ከሆነ ታዲያ በአፄ ፋሲል ዘመን እንዴት በእንፍራዝ ውስጥ ሊኖር ቻለ?”
እያንዳንዳቸው ዘርዓ ያዕቆብ እንዴትም ሆኖ አውሮፓዊ (ፈረንጅ) ሊኾን አይቻልም፤ አይደለም፣ ኢትዮጵያዊ እንጂ የሚሉ ናቸው፡፡ ማነው ፈረንጅ ያለው? “ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ነበረ ወይ?” ብሎ መጠየቅ፣ “ዘርዓ ያዕቆብ ፈረንጅ ነው፣” ማለትን ያመላክታል? በጭራሽ፣ ያልተባለውን በመያዝ ነው ደረጄ የደከሙት፡፡
እኔ ያልኩት፣ “ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል በእውን ዓለም በምድር ላይ የኖረ ሰው አልነበረም” ነው። የዘርዓ ያዕቆብ መጽሐፍም ዘርዓ ያዕቆብ የተባለ ፈላስፋ ገጸ ባሕርይ ተፈጥሮ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በአፄ ሱስንዮስና ፋሲል ዘመን የተነሳ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ተደርጎ የቀረበበት ነው፡፡ ምናልባትም ጸሐፊው ልብ ወለድ ልጻፍ ብሎ የጻፈው መኾን አለመሆኑ ሊጠየቅ ቢችልም፣ ያልተዋጣለት ልብወለድ፣ የልብ ወለድነት መጠንን ያልያዘ ልብወለድ ሠራ ነው። … ይህ ነበር የኔ ሀሳብ፡፡ ስለዚህ ከ ፩ - ፮ ያሉት በሙሉ፣ ምንም እንኳን በዚያም ቢሆን ምንም ያህል ውጤት የማያስገኙላቸው ቢሆኑም፣ ዘርዓ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ እንጂ ፈረንጅ ሊባል አይገባውም ለማለት የቀረቡ ናቸውና ከኔ ጋር የሚገናኙ አይደሉም፡፡ ነገር ግን አሁንም የጸሐሀፊውንና የአንባቢውን ግርታ ለማስወገድ ሲባል ተራ በተራ እያነሳሁ እነዚህኑም ቢኾን እመለከታቸዋለሁ፡፡
አንድ፡- “ዳዊት ለ ፫ ወር፣ ቅኔ ለ፬ ዓመት፣ የመጻሕፍት ትርጉም ለ ፲ ዓመት…” ሊኖር የሚችለውን መከራ ታግሶ ለመማር የሚችል አውሮፓዊ ሊኖር እንደማይችል ያስደመደመው ይህ ዘርዓ ያዕቆብ ራሱ ስለራሱ የገለጸው ቆጠራ ነው፡፡
በሚያስገርም ሁኔታ የዚህ አገላለጽ ዘይቤ በራሱ ይህ ሰው የአብነት ት/ቤት ደርሶ የማያውቅ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በት/ቤቱ ያለፉ ሁሉ ሊመሰክሩት የሚችሉት ነው፡፡
የ፫ወር የዳዊት ትምህርቱን ከ ፬ ዓመቱ ግዕዝና ከ፲ ዓመቱ መጻሕፍት ጋር በቅደም ተከተል ማሰለፉ ብቻ ሳይሆን በነዚህ መስመር ያለፈ ሰው አገላለጽ እንዳልሆነም ሊታወቅ ይችላል፡፡ ሊባል የተፈለገው በትክክለኛ የቤቱ ቃሎች አልተገለጹም። “ዳዊት ደገምሁ፣ ይህን ያህል ጊዜ ዘለቅሁት ወይም ወጣሁት፣ ነው የሚባለው፡፡ ፀሐፊው በዚያ ቢያልፍ ኖሮ አፉም፣ መጻፊያውም እሺ አይለውም ነበር “ዳዊት ተማርሁ” ለማለት፡፡
ይበልጥ እንበርብር ካልን እኮ ዳዊት የደገሙበት ወሮችንም የመቁጠር ልማድም የለም  ት/ቤቶቹንም ሲጠሩዋቸው ይለያሉ፡፡
“በቅኔ ቤት፣ በመጻሕፍት ቤት …” እያሉ ይናገሯቸው እንደሁ እንጂ እንዲያ “ግእዝ ፣ ቅኔ በመማር” ፣“የመጻሕፍት ትርጓሜ በመማር” ተብሎ መገለጹ ስህተት ነው ባይባልም በነሱ ዘንድ ያልተለመደ፣ በሩቅ ያለ የኛ ብጤው የሚገልጽበት አገላለጥ ነው፡፡ ቅኔም “ተማርኩ” አይባልም፤ “ቆጠርኩ፣ ቀጸልኩ፣ ዘረፍኩ፣ አደላደልኩ፣ አስነገርኩ፣…” ዓይነቶቹን እንጂ፡፡ “ተማርኩ” ቀድሞ ነገር ባፋቸውም አይገባም፡፡
ቅኔውንና መጻሕፍቱን ከመቁጠሩ እስከ ከፍተኛው ደረጃ ወይም እስከምን ድረስ እንደተጓዘበት ባይገልጽልንም ከማን ዘንድ እንደተማራቸው ሳያስቀድም መቅረቱም አጅሬ ለቤቱ ባዕድ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ይህ ለነሱ መማር ዋነኛው አስረጋጩ ነገር ነው፡፡ ባህላቸውና ልማዳቸውም ነው፡፡
የመጻሕፍት መምህርነቱን የሚናገረው ገጸ-ባህርይ ዘርዓ ያዕቆብ በየትኛው ዘርፍ እንደሆነ አይነግረንም፡፡ ዝም ብሎ የመጻሕፍት መምህር አይባልም፡፡ መጋቤ ብሉይ? መጋቤ ሀዲስ? ወይስ የሊቃውንቱና የመነኮሳቱ? ከነዚህም ሌላ ሕግጋት ምናልባትም የቁጥር ትምህርት የሚባሉ አሉ። በየትኛው ነው ያ ሰው ጉባኤ የዘረጋው? በ፬ቱም የተመሰከረለት እኮ “፬ዓይና” ይባላል፡፡ ይህን የመሰለ ማዕረጉን ትቶ ይጽፋል? ከ፬ ዓይና ውጭ ነው ብንል “መጋቤ ብሉይ፣ መጋቤ ሀዲስ” ይባላል፡፡ ይኽ ጸሐፊም የራሱን ጉባኤ የዘረጋ ከሆነ ከነዚህ አንዱን በሆነ ነበር፡፡ ከሆነም ደግሞ በጻፈው ነበር፡፡ ግና ልብወለድ ነውና ይሄ ይሄ ቀዳዳ ሁሉ ይገኝበታል፡፡
ደግሞስ በ፲ ዓመት የተወሰነው የመጻሕግት ተምህርት የትኛው ነው? ሙሉው እኮ በትንሹ ፳ዓመት ነው የሚፈጀው! ቢያንስ ሁለቱን ያህል ይጨርስበት ይሆናል፡፡ ግን ይህን ለማወቅ ስላልቻለ እንዳለ “መጽሐፍ” ብሎ ዘጋው፡፡ ባጠቃላይ ይህ የመጀመሪያው ነጥብ ይበልጥ ዘርዓ ያዕቆብ የተባለው አብነት ት/ቤትን በስማ በለው የሚያውቀው መሆኑን ነው የሚገልጸው፡፡
ሁለት፡- ዘሩን ከካህናት፣ ከደኃ ወገን… ይቆጥራል ይላል ራሱ ስለቆጠረ እንዴት መሟገቻ ሆኖ ይቀርባል? ደግሞስ እንዴት ያለ ማያያዝ ነው፣ “ዘሩን ከካህንና ከደኃ ወገን የሚቆጥር ፈረንጅ ይኖራል ወይ?” ብሎ ጥያቄ? ...
ሦስት፡- ስለ ሀሳቡ አደረጃጀትና አቀራረብ ይነሳል፡፡ ብዙዎች አውሮፓዊ ነው የሚሉት የሐሳቡን አደረጃጀትና አቀራረብ በማየት ነው ይላሉ፡፡ የዘርዓ ያዕቆብን ፍልስፍና ያን ያህል ጥሩ የሚባል እንዳልሆነም ጠቁመው በኢትዮጵያ ከዚህም የበለጡ ፍልስፍናዎች እንዳሉ ገልጸዋል። በዚህስ ከኔም ጋር ይስማማሉ፤ እኔም ይህንኑ ነበር የገለጽሁት፡፡ ነገር ግን የተጠቀሙበት ላይ እንለያያለን፡፡ እርሳቸው ለፈረንጆቹ ጸሐፊዎች የሚሆን መሟገቻ አድርገውታል፡፡ በእርግጥ ይሆናል ግን፣ “ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ነበር፣” ለማለት ግን አያስችልም፡፡
አራት፡- አውሮፓዊ ቢሆን ኖሮ ሽሽቱ ወደ ቀይ ባህር እንጂ ወደ ዋሻ አልነበረም፡፡ ይህም እንደ አንድ መከራከሪያ የቀረበ ነው፡፡ ወደየትም ይሽሽ፣ ቀድሞ ነገር ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ሲኖር አይደለም? ጸሐፊው እኮ ኢትዮጵያዊ ገጸ ባህርይ ነው ያቀረበው፡፡ ስለዚህ ማድረግ ያለበትን አድርጓል። ወደ ውጭ ከማሸሽ እዚሁ ተደብቆ እንዲኖር ዋሻውን ፈጠረለት፡፡ አለቀ፡፡ ኢትዮጵያዊ አድርጎ ነውና ሊያቀርብ የሞከረው፡፡  
አምስት፡- የዳዊቷ ነገር መጣች፡፡ ዳዊት በኢትዮጵያውያን ጸሎት የማትቀር መሆኗ! ይህንንም ነው የዘርዓ ያዕቆብም ጸሐፊ የተመለከተው። ይልቅስ ደረጄ አንድ በቤቱ ያለ ጥሩ ልማድ አንስተዋል። በቃላችን ብናጠናው ከሰስህተትና ከግድፈት ለመዳን በመጽሐፍ እንደግማለን፣” ብለዋል …
ልክ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ በቃል ትምህርት ብቻ ለያዙት እንጂ ለመጻሕፍት ሊቃውንት አይሆንም፡፡ ቀድሞ ነገር ነውር ነው፡፡ ውርደት ነው፡፡ ትምህርቱን ያላደላደሉት መሆኑን ማስመስከሪያ ነው፡፡
ስድስት፡- ወደ ታሪክ የሚገባ ሐሳብ ይቀርባሉ። መጽሐፉ የተጻፈው በፋሲል ዘመን ነው፤ ያን ጊዜ ደግሞ ፈረንጅ ከሀገር ተባርሯል፡፡ እና ከየት የመጣ ፈረንጅ ነው በእንፍራዝ ተቀምጦ የሚገኘው?
ደረጀ ኅብስቱ አሁንም እዚያው ናቸው፡፡ መጽሐፉ በፋሲል ዘመን እንደተጻፈ ስለሚያስገነዝብ የትኛው ፈረንጅ ነው በዚያ ዘመን የነበረው ይሉናል። በፋሲል ዘመን ለመጻፉ ከራሱ ዘርዓ ያዕቆብ ከተባለው ገጸ ባህርይ ቃል ውጭ ምንም ነገር የለንም፡፡ እርሱ ደግሞ ወደኋላ ሄዶ ፬፻ እና ፫፻ ዘመን አይደለም ፬ሺ እና ፫ሺ ዓመት ላይ ሊያስቀምጠው ይችላል፡፡ መጽሐፉ ግን የተጻፈው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ስለመሆኑ በጊዜው ከነበሩ ሰዎች የተጻፈው ብቻ ይበቃል፡፡ (“ገድለ ያዕቆብ” በሚል ርእስ ስለ ጃኮቢስ ገድል አባ ተክለሃይማኖት በተባሉ የአድዋ ካቶሊካዊ መነኩሴ የተጻፈውን ያንብቡ፡፡ በጊዜው በሕይወት የነበሩና በጊዜው የሆነውን የጻፉ ናቸው፡፡)   
ከዚህ ውጭ በመካከል ክላውድ ሳምነር የዘርዓ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊነት አልተጠራጠሩም የሚል አስገብተዋል፡፡ “ክላውድ ሳምነር በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ እድሜያቸውን የፈጁ” መሆናቸውንም በመጥቀስ ነው ደረጄ ይህን ያስገቡት፡፡ እንዲህ ከኾነ ይህን የማይረባ ፍልስፍና ትተው ራሳቸው ደረጄ ረቀቅ-መጠቅ ያሉ መኾናቸውን የገለጿቸውን ለምን መርምረው አላገኟቸውም? ነገሩ ግን ወዲህ ነው ክላውድ ሳሞነር ፊትለፊት የገኟቸውን ብቻ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ብለው፣ ፍልስፍናው ላይ ትኩረት አደረጉ እንጂ ብዙም በዚህ ነገር ላይ አልገቡበትም፡፡
በአጠቃላይ አሁንም ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ላለመኖሩ ምንም ዓይነት መረጃና ማስረጃ (መጽሐፍ ተብሎ በስሙ ከቀረበለት ውጭ) አናገኝም.. መጽሐፉም ዘርዓ ያዕቆብ ምናባዊ ሰው መሆኑን ነው እያሳየን የሚገኘው፡፡
ደረጄ ጽሑፋቸውን ሲጀምሩ፣ ይኼው ዘርዓ ያዕቆብ እንዳለው ተደርጎ በመጽሐፉ የቀረበውን፣ ወሐሳዊ ብእሲሰ ዘየኅሥሥ ንዋየ አው ክብረ...። የሚለውን በመጥቀስ የቀረበው ዝርዝር ግን እኔን ይመለከት እንደሆነ እንዲሁ በድፍኑ “ያለመተዋወቅ!” ብዬ እተወዋለሁ፡፡


Published in ባህል

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰሚ ጠፋሳ! የተበላሸ ነገር ሲጠቆም… የመፍትሄ ሀሳብ ሲቀርብ… “ኧረ ቤቶች!” ሲባል እህ ብሎ የሚያዳምጥ፣ “አቤት…” ብሎ በር የሚከፍት ተመናመነብንሳ! እርስ በእርሳችን ያለን አመለካካት ከመዛባቱ የተነሳ ነገራችን ሁሉ.. አለ አይደል… ዶፉን እንኳን እየለቀቀው “ኧረ ዝናቡ ልብሱን አበሰበሰው፣ ወደ ውስጥ አስገቡት…” ሲባል ነገርዬው “ስለ ልብስ መበስበስ አንተ ነሀ የምትነግርኝ!” አይነት ‘ዝምታ’ እግር ተወርች እያሰረን ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በቃ፣ “‘ሞዴሊስት’ አይባልም…” “‘ዋይኔ’ ሩኒ አይባልም….” “ኒውዘርላንድ’ አይባልም…” እንዲህ አይባልም፣ እንዲያ አይባልም ቢባል ሰሚ ጆሮ ጠፋ አይደል!… “ምን ይባል፣ ምን አይባል ማነው ለእኔ የሚነግረኝ…” አይነት ‘ዝምታ’ ውጦ ነው፡፡ (አንዳንድ የስፖርት ጋዜጠኞች እኛ በምንከታተለው ቲቪ የሚመጡ ዘጋቢዎች “ዌይን ሩኒ” ሲሉ፣ እናንተ በምትከታተሉት ቲቪ የሚወጡ ዘጋቢዎች “‘ዋይኔ’ ሩኒ…” የሚሉት…እኛን ማጋጫታቸው ነው እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… እንኳን ቁማር ይወዳሉ የሚባሉት… አባቱ ናቸው አጎቱ… አልሰሙን! አሀ…ልክ ነዋ…“እንወራረድ ዌይንዬን ሀበሾች ‘ዋይኔ’ እያሉ ነው የሚያቆላምጡት…” ብለው ሊወራረዱ ይችሉ ነበራ!)
ይሄ ‘ሞዴሊስት’ የሚሉት ነገርማ…ራሳቸው በሞዴሊንግ ኢንደስትሪው ውስጥ ያሉ ሰዎች ሲደጋግሙት ግራ ግብት አይላችሁም! ነው ወይስ ሞዴሊስት ልማታዊ ሞዴል የኒኦ ሊበራሎች ሆኖ ነው! (ምን እናድርግ ዘንድሮ…እንትን ያልናት ሁሉ በልማታዊነትና በኒኦ ሊበራሊስትነት ሚዛን እየተቀመጠች ግራ ገባን! “እኔን ግራ ይግባኝ…” የሚል በሌለበት ዘመን…አለ አይደል… ግራ ከመጋባት ይሰውራችሁ!)
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን፣ “ፌይንት ሠራሁ…” ምን ማለት ነው? ምንም ይሁን ምን ከ‘ሞዴሊስት’ ይሻለኛል፡፡
ደግሞላችሁ…“በጉዳዩ ‘ኢንተረስቲንግ’ ነኝ…” የምትለዋ ትስማማኛለች፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…“እህ!” የሚል እየጠፋ፣ ነገርዬው ሁሉ የ‘ሞዴሊስት’ እና ‘ዋይኔ’ ሩኒ ነገር ሆነብን!
የምር እኮ… ላይ የሰንበቴ ጌሾ ማስጣት የሚችለው ወንበር ላይ ከሚቀመጡት፣ እታች ከአቧራው ጋር አብረን እየቦነንን ያለነው ሁላችን…“እህ…” ብሎ መስማት ይቅርታ የማይደረግለት ሀጢአት ነገር እያደረግነው ነው፡፡
“እዚህ ቦታ የጎደለ ነገር አለ…” “እዛ ቦታ የተዛባ ነገር አለ…” ሲባል እህ ብሎ ለማዳመጥ ፈቃደኛ አለመሆን ‘ብሔራዊ መለያ’ አይነት ነገር እየሆነ እኮ ነው!
“ኧረ እዚህ ቦታ ውሀ ከጠፋ አምስት ቀኑ፣ ውሀ ጥም ማለቃችን ነው…” ሲባል ማን ሰምቶ!
“ኧረ በሞባይል ከመደዋወል ከቦሌ ጉለሌ የምንፈልገው ሰው ያለበት መሄዱ እየቀለለ ነው…” ብንል ማን ሰምቶ! (ይልቁንም እንደ ልባችን ማግኘት ባቃተን አገልግሎት… ስለ ‘ልዩ ቅናሽ’ ዕድሎች ይነገረናል፡፡)
“ኧረ እዚህ ቦታ ቧንቧ ፈንድቶ መፍሰስ ከጀመረ ሳምንቱ…” ሲባል ማን ሰምቶ!
“ኸረ ከተማዋ ቆሸሻ፣ ለነዋሪም የጤና ቀውስ ለጎብኚም ‘የዕይታ ቀውስ’ እየፈጠረች ነ”ው…” ሲባል ማን ሰምቶ! (ይልቁንም ስለ አፍሪካ ዋና መዲናነቷ፣ እየዘመነችና እያሸበረቀች ስለ መሆኗ እንሰማለን!)
“ኧረ ታክሲው ከፍጥነት በላይ ነው እየበረረ ያለው፣ ሾፌር ረጋ በል…” ሲባል ማን ሰምቶ! (ይልቁንም… አለ አይደል… በቀደም አንድ ፕሮግራም ላይ እንደሰማነው በምሽት መሀል መንገድ ላይ መኪናውን አቁሞ “ከፈለጋችሁ ወረዱ…” አይነት መልስ ነው የምናገኘው፡፡
እናላችሁ…“እህ!” የሚል እየጠፋ፣ ነገርዬው ሁሉ የ‘ሞዴሊስት’ እና ‘ዋይኔ’ ሩኒ ነገር ሆነብን!
ሀሳብ አለን… ለዓለም አቀፍ የአእምሮ ንብረት ምናምን ድርጅት ማመልከቻ ይግባልን፡፡ ልክ ነዋ…. እነሱ ጤፊቷን ‘ሊወስዱብን’ ዳር ዳር እያሉ አይደል…እኛም ‘ሞዴሊስት’ እና ‘ዋይኔ’ ሩኒ የሚሉት አጠራሮች  በእኛ የአእምሮ ንብረትነት ይመዝገቡልን። በሌላ አገር እንደዚህ ስለመባሉ የምናውቀው ነገር የለማ!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ሰዎች አለቃ ሲሆኑ የሚባሉትን ለመስማት የሚከብዳቸው ለምንድንው? ነው ወይስ እዚህ አገር ብቻ ድምጽ ከ‘ታች ወደ ላይ’ አይጓዝም እንዴ! ልክ ነዋ…ምንም ነገር እዚች አገር ሲገባ ‘ሞዲፋይድ’ ስለሚሆን (ቂ…ቂ…ቂ…) የድምጽ ሞገድ አካሄድም ‘አገሪኛ ተች’ ተሰጥቶት እንደሆነ ብዬ ነው፡፡ ስሙኝማ… “መጠጥ ከድራፍት ወደ ብሉ ሌብል ሲለወጥ የመስሚያ ህዋሳቶችን ይተናኮላል…” ምናምን የሚል ‘ጥናት’ የሰማ ሰው ካለ ሹክ ይበለኝማ! (እንትና ‘ጎልድ ሌብሉ’ ጠርሙሱ ስንት ነበር ያልከኝ? ለምን ይዋሻል… የእንትንን አውራጃ ህዝብ ቁጥር የነገርከኝ መስሎኝ ነበር!)
እኔ የምለው ቴሌ አንዳንዴ ወይ ለመልካም ምኞት መግለጫ  ወይ ጠንቀቅ በሉ ለማለት የሚልካቸውን የጽሁፍ መልእክቶች ልብ ብላችሁልኛል! ይሄ ኬብሉ ምናምን ሲቆራረጥ “በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች የተነሳ…” ምናምን ይባላል፡፡ እኔ የምለው…እነኚህ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ‘የቴሌ እንግሊዘኛ’ ላይም መመላለስ ጀመሩ እንዴ! (ቂ…ቂ…ቂ…) ኧረ እባካችሁ…አታሳጡን! ይቺን እዩልኝማ…
(Please don’t respond to fraud text/SMS falsely sent using +228 & other country code as if you would win a lottery/gift or selected for award. Ethio telecom)
እናላችሁ…እኛ ብዙ ባይገባንም ይሄን የሚያክል ግዙፍ ድርጅት ከዚህች ሻል ያለች የ‘ፈረንጅ አፍ’ መጻፍ አቃተውሳ! ነው… ወይስ ኮንትራቱ ሁሉ ወደ ምሥራቅ ሲሄድ ‘የፈረንጅ አፍ’ም ወደ ምሥራቅ ዘመም ማለት ጀመረች! ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…አይገርማችሁም…ለምንድነው “እህ…” ብለን የምንሰማ ቁጥራችን እንደ ኑሯችን ቁልቁል የሆነው!
የተበላሸ ነገረ እየታየ፣ መስመር የለቀቀ ነገረ እየታየ… “ኧረ ይሄን ነገር አንድ በሉት…” ምናምን ሲባል…. ‘ቄሱም መጣፉም’ ጭጭ!  እናላችሁ የሚሰማ እየጠፋ ነው፡፡ አሁንማ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ድፍን አገር ጉድጓድ ምሶ ያደፈጠ ነው የሚመስለው፡፡ ልክ ነዋ… በየቀኑ የምንሰማቸው፣ የምናያቸውና ያየንና የሰማን የሚመስሉን ነገሮች በዝተው አደነዘዙና!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ….ኳስ ተጫዋቾቹ ‘ውራ’ ሆነው የተመለሱበት ቻን ከመሄዳቸው በፊት “ብናሸንፍ ስንት ሽልማት ትሰጡናላችሁ?” ብለው ጠይቀው ነበር የሚሉት ነገር ግርም አላላችሁም! የምር ‘የጉድ ዘመን’ ቢባል አይበዛበትም፡፡
ኮሚክ እኮ ነው… ለአፍሪካ ዋንጫ ዋዜማ እኮ “የተገባልን ገንዘብ አልተሰጠንም…” ምናምን ተብሎ የልምምድ አድማ ነገር ነበር፡፡ ያን ሰሞን እኮ… እኛም የሚዲያ ሰዎች…አለ አይደል… በሌሎች አገሮች ተጫዋቾች የጠላነውና ሲሰቀጥጠን የኖረ የአገርን ጉዳይ በ‘እርግጡን ተናገር’ መደራደር እኛው ዘንድ መጣና አረፈው!… ከማለት ይልቅ “ቶሎ ስጧቸው እንጂ!” አይነት ነገር ውስጥ መግባታችን… የሚታዘበን ቢኖር ኖሮ አስተዛዛቢ ነበር፡፡
“አይ አገር አይ አገር ኢትዮጵያ…” ምናምን የሚል ዘፈን ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ ለዓለም ዋንጫ የደረስንበት መድረሱ በታሪካችን ታይቶ የማይታወቀ እንደሆነ ሁሉ፣ ባንዲራ ለብሶ አገር ለመወከል ስንት ትበጥሳላችሁ አይነት ነገርም ያየንበት ጊዜ ትዝ አይለንም፡፡ (ይቺ አገር ተጠብቃ እዚሀ ድረስ የዘለቀችልን በሰላም አደባባይም ይሁን በጦር ሜዳ ‘በባንዲራዋ ስር’ አገልግሎት ለመስጠት “መጀመሪያ በሂሳቡ እንስማማ…” በማለት አይደለም፡፡
እናማ…የእግር ኳሳችን ነገር በአሰልጣኞች ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት መዛባቱ፣ በተጫዋቾች ዕድሜ ሽወዳ… ምናምን ብቻ ሳይሆን መስተካካል ያለባቸው ብዙ ነገሮች ያሉ አይመስላችሁም፡፡ (“ሜዳሊያ ብናመጣ ስንት ትበጥሳላችሁ…” ሳይሉን በየኦሎምፒኩ መድረክ፣ በየዓለም ሻምፒዮና አንገታችን ቀና እንዲል የሚያደርጉን አትሌቶቻችን ክብር ምስጋና ይድረሳቸው፡፡)
እናላችሁ…በእግር ኳስም ነገርዬው የሚሰማ አልገኝ እያለ ተቸግረናል፡፡ ከስር በመቶ የሚቆጠሩ የተዋጣላቸውን ተጫዋቾች ኮትኩቶ ስለማምጣትና የዛሬ አምስትና ሰባት ዓመት ከማንኛውም አገር እግር ኳስ ቡድን ጋር የሚስተካካል ቡድን ስለመገንባት ከማሰብ ይልቅ አሁንም የ‘ዕቅዳችን አድማስ’ ከሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ “ኧረ እባካችሁ ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት እከሌ ይምጣ እከሌ ይቅር ከማለት ይልቅ በመላ አገሪቱ ውስጥ በወጣቶች ላይ ሥራ ይሠራ ሲባል…ማን ሰምቶ! ዘፈናችን “ሁልጊዜ አበባዬ…” ነገር ሆነብን፡፡
(በነገራችን ላይ በወከባው ውስጥ ሰምጠው ሳይቀሩ፣ “የአገር ጉዳይ ነው…” በሚል ሽፋን ቀሺሙን “አሪፍ ነው…” ሳይሉ ስለ ረጅም ጊዜ ዕቅድ አስፈላጊነት ሲናገሩ የዘለቁ የሚዲያ ሰዎች መኖራቸው አሪፍ ነው፡፡ በዚሁ ቀጥሉማ!)
እናላችሁ…ነገርዬው ሁሉ የ‘ሞዴሊስት’ እና ‘ዋይኔ’ ሩኒ ነገር ሆነብን!
“መከራው ያላለቀለት በሬ ከሞተ በኋላ ቆዳው ነጋሪት ይጠፈራል” የሚሏት አባባል አለች፡፡ ከዕድለ ቢሱ በሬ ዕጣ ፈንታ ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Page 5 of 13