ከሁለት ዓመት በላይ ማሲንቆዬን ሰቅዬ ድንጋይ ተሸክሜአለሁ
ከማሲንቆ ውጭ አልሞክርም፤ በማሲንቆው ግን የሚያህለኝ የለም
ማሲንቆ ከልጅነት እስከ እውቀት
አብሮኝ ያደገ ነው

አባትሽ ማሲንቆ ተጫዋች ነበሩ፡፡ የእርሳቸው ተፅዕኖ አድሮብሻል ማለት ይቻላል?
በትክክል! አባቴ ጐበዝ ማሲንቆ ተጫዋች ነበር። የሚወዳደረው አልነበረም፡፡ እኔም በልጅነት አዕምሮዬ ማሲንቆውን ስሰማው በጣም ይማርከኝ ነበር፡፡ እናም በትክክል ተፅዕኖ አሳርፎብኛል፡፡
አባትሽ ማሲንቆ የሚጫወቱት በመተዳደርያነት ነው ወይስ -----
አባቴ ማሲንቆ የሚጫወተው ለግል ስሜቱ ነበር፡፡ ሲጫወት ብር ተከፍሎት አያውቅም፡፡ ያ ማለት ማሲንቆ ጨዋታ መተዳደሪያው አልነበረም ማለት ነው፡፡ ዋና መተዳደሪያው ግብርና ነው፤ ጐበዝ ገበሬ ነበር፡፡
የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድንን መቼና እንዴት እንደተቀላቀልሽ ታስታውሻለሽ ?
በደንብ አስታውሰዋለሁ፡፡ በ1971 ዓ.ም ነው የተቀላቀልኩት፡፡ በወቅቱ የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አርቲስት ቀለመወርቅ ደበበ አሳይታ፤ ለስራ መጥተው በአጋጣሚ አገኙኝና አነጋገሩኝ፡፡  ሴት ማሲንቆ ተጫዋች በማየታቸው የተገረሙ ይመስለኛል፡፡ ከዚያም ከአሳይታ ወደ ደሴ ይዘውኝ መጡና ከቡድኑ ጋር ተቀላቀልኩኝ፡፡
ቀደም ሲል እንደነገርሽኝ ትውልድና እድገትሽ ወረባቦ ነው፤ በምን ምክንያት አሳይታ ገባሽ?
አሳይታ የገባሁት ማሲንቆዬን ይዤ ነው፡፡ ማሲንቆ ጨዋታ በደንብ ከጀመርኩ በኋላ ለማሲንቆ ያለኝ ፍቅር እየጨመረ መጣ፡፡ በዛን ወቅት ሴት ልጅ አግብታ፣ ትዳሯን መምራት፤ ልጅ ወልዳ ማሳደግ እንጂ ያውም በወንዶች ብቻ የተለመደውን ማሲንቆ ይዛ አደባባይ መውጣትና መጫወት የማይታሰብ ነበር---እና የአካባቢው ሰው ጥሩ አመለካከት ስላልነበረው፣ ማሲንቆዬን ይዤ ወደማልታወቅበት በረሃ ገባሁ፡፡ እዛ እያለሁ ነው አርቲስት ቀለመወርቅ አግኝተው ያመጡኝ፡፡
አሳይታ ሳለሽ የአንቺን ማሲንቆ ለመስማት ህዝብ ይጐርፍ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ መተዳደሪያ ስራ አድርገሽው ነበር እንዴ?
አዎ! በየቡና ቤቱ  እየተዘዋወርኩ፣ እየተከፈለኝ እጫወት ነበር፡፡ ብዙ ሰው የምሰራበት ቡና ቤት ይመጣ ነበር፡፡ እኔም ሴት ነኝ ብዬ ሳልሸማቀቅ በደንብ ነበር የምጫወተው፡፡ ማሲንቆን በመጫወት የሚታወቁት ወንዶች በመሆናቸው፣ እኔን ለመጀመሪያ ጊዜ ስጫወት ሲያዩ ትንግርት ይሆንባቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ብዙ ሰው ተሰብስቦ ማሲንቆዬን ይሰማ ነበር።
የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድንን ከተቀላቀልሽ በኋላ የነበረሽ ቆይታ ምን ይመስላል?
ቡድኑን ከተቀላቀልኩ በኋላ በደሞዝ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ፡፡ ከቡድኑ ጋር ጥሩ መግባባትና  ቆይታ ነበረኝ፡፡
ደሞዝሽ ስንት ነበረ? ረስተሽው ይሆን?
(ረጅም ሳ…ቅ) ስንት ነበረ እናንተዬ? 185 ብር ይመስለኛል--- እንደዛ ነበር ደሞዜ፡፡
እስኪ ስለግል ህይወትሽ እናውራ፡፡ ትዳር ይዘሽ ነበር? ልጆችስ አፍርተሻል?
ትዳር ነበረኝ፤ ልጆች ግን አልወለድኩም፡፡
የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን በ1983 ዓ.ም ተበትኖ ሁላችሁም ተለያይታችሁ ነበር፤ እስቲ ስለእሱ ጉዳይ አጫውቺኝ -----
እስካሁን ለምን እንደተበተንን እኛም ምክንያቱን አናውቀውም፡፡ በለውጡ ጊዜ “ላልተወሰነ ጊዜ ከስራችሁ ታግዳችኋል” በሚል  አንድ መስመር ደብዳቤ ከስራ ታገድን፤ ከዚያም ተበታተንን፡፡ እኔም አዲስ አበባ ሄጄ በዚያው ቀረሁ፡፡
አዲስ አበባ ምን ትሰሪ ነበር?
የቀን ስራ ነበር መስራት የጀመርኩት፡፡
የቀን ስራ ስትይ ድንጋይ መሸከም ነው? ልብስ ማጠብ ወይስ---
ድንጋይ እሸከም ነበር፡፡ መጀመሪያ ስራውን ስጀምር ለሚያሰሩኝ ሰዎች አልበሜን እንዲያስቀምጡልኝ ሰጥቻቸው ነበር፡፡ ሃላፊዎቹ አልበሜን ሲያገላብጡ ከላሊበላ ኪነት ቡድን ጋር የነበረኝን ፎቶ፣ በስራ ላይ እያለሁ የተነሳሁትን ሁሉ አገኙት፡፡ ከዚያም የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን አባል መሆኔን አወቁ፡፡ በኋላ በፍፁም እዚህ ድንጋይ መሸከም የለባትም አሉ፡፡ ከዚያም ከድንጋይ መሸከም አወጡና ወደ ስቶር አስገቡኝ፡፡ በድንጋይ መሸከም ብቻ ከሁለት አመት በላይ ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያ ስቶር ኪፐር ሆኜ ነው የቆየሁት፡፡
ግን እኮ አዲስ አበባ ውስጥ የባህል ምሽት ቤቶች---- አዝማሪ ቤቶች ሞልተዋል፡፡ ድንጋይ ወደ መሸከም ከመሄድሽ በፊት በየምሽት ቤቶቹ ለመስራት አልሞከርሽም?
አልፈለግሁም፡፡ ያኔ ፍላጐቴ እራሴን መደበቅ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር ይሰሩ የነበሩት የቡድናችን አባላትና ጓደኞቼ አብዛኞቹ አለቁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከእኔ አጨዋወት ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ  ባለሙያ አላገኝም፡፡ እኔ ለማሲንቆዬ ክብር እሰጣለሁ፡፡ ብር ለማግኘት ስል ካልሆነ ባለሙያ ጋር ከምሰራ ብዬ ነው ማሲንቆዬን ሰቅዬ ወደቀን ስራ የገባሁት፡፡
መጀመርያ በ1983 ዓ.ም “የቀድሞ መንግስት ደጋፊዎች ናችሁ” በሚል እንደተበተናችሁ ይነገራል። ከዚያ በኋላ በሼህ ሁሴን አሊ አላሙዲን ድጋፍ እንደገና ወደ አዲስ አበባ ሄዳችሁ ብትደራጁም ድጋሚ መበተናችሁን ሰምቻለሁ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የተበተናችሁበት ምክንያትስ ምንድን ነው?
እኔ በበኩሌ የዚህንም ምክንያት አላውቀውም፡፡ ግን የአበታተናችን  ሁኔታ ከቀድሞው ጋር ተመሳሳይ ነበር - “ላልተወሰነ ጊዜ” በሚል ነው፡፡
ሼህ አላሙዲን ካደራጇችሁ በኋላ ሥራ ጀምራችሁ ነበር?
አዎ ጀምረን ለሰባት ወራት ያህል ሰርተን ነበር፡፡ ግን ቅድም እንዳልኩሽ ባላወቅነው ሁኔታ “ላልተወሰነ ጊዜ ከስራ ታግዳችኋል” በሚል ነው የበተኑን፡፡ ከዚያ እኔን ሸበሌ ሆቴል ስራ ያሰራኝ ጀመር፡፡ ማሪቱ ለገሰ አዲስ አበባ ምሽት ቤት ከፍታ እዛም ትንሽ ሰራሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ወደቀን ስራው የገባሁት፡፡
የማሪቱ የምሽት ቤት ስራ በምን ምክንያት ቆመ?
ማሪቱ ዘግታው አሜሪካ ሄደች፤ እኔም በዚያው ስራ አቆምኩኝ፡፡
አንቺ ከልጅነት እስከ እውቀት በሙዚቃ ውስጥ የኖርሽ እንደመሆንሽ፣ ኑሮን ለማሸነፍ የገባሽበት የቀን ስራ -- ድንጋይ ሸክም ፈተናው ምን ይመስል ነበር? እስቲ ስሜቱን ግለጭልኝ ---
ከባድ ነው ግን አለፍኩት፡፡ እንዴት አለፍሽው ብትይኝ ---- በሙዚቃው ተስፋ ቆረጥኩና ያገኘሁትን ሥራ እየሰራሁ ኑሮዬን መግፋት እንዳለብኝ ራሴን አሳመንኩት፡፡ ስጀምረው ትንሽ ተማርሬ ነበር፣ በኋላ ለመድኩት፡፡ አሰሪዎቼ እግዜር ይስጣቸውና ---- ማንነቴን ሲያውቁ ወዲያውኑ ወደ ስቶር አመጡኝ፤ ትንሽ ቀለል አለኝ፡፡
የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም እንደገና ሲደራጅ አንቺን ማግኘት አልቻሉም ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ቡድኑ ከተቀላቀልሽ ወደ አራት ወር ገደማ ሆኖሻል፡፡ እንዴት ሊያገኙሽ ቻሉ?
የሸገር ሬዲዮ ጋዜጠኞች የቀን ስራ ስሰራ አግኝተው ቃለ ምልልስ አደረጉልኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ይሄን የሰሙ ሰዎች ፈልገው አገኙኝና እንደገና ከቡድኑ ጋር ተቀላቀልኩኝ፡፡
አንቺን ፈልገውሽ ሲመጡና ሲያገኙሽ ምን ተሰማሽ ?
እኔ ማመን አልቻልኩም፡፡ ደስታዬን መቆጣጠር አልቻልኩም፤ እንደገና የተፈጠርኩ ነው የመሰለኝ፤ እነሱም ፊት ለፊት በአካል እስኪያዩኝ እውነት አልመሰላቸውም ነበር፡፡
ድጋሚ አገኛቸዋለሁ የሚል ተስፋ ነበረሽ?
በፍፁም! ለምን? አብዛኞቹ ሞተዋላ! ከድሮዎቹ ብዙዎቹ ስላለቁ በህልሜም በእውኔም አላሰብኩትም ነበር፤ ግን እግዜር ፈቀደና ተገናኘን፡፡
በፊት አብረውሽ ከሰሩት የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን አባላት ስንቱን አገኘሽ?
ሁለቱን ሙሀመድ ከመከምንና ጋሽ አራጌን ብቻ ነው ያገኘሁት፡፡ በቃ ሶስታችን ነን በህይወት ያለነው፡፡  ማሪቱም አሜሪካ ነው ያለችው፡፡
በፊት ስንት ነበራችሁ?
27 ያህል ነበርን፡፡
እስቲ እነማን እነማንን ትጠሪልኛለሽ?
ዚነት ሙሃባ፣ የማሪቱ ለገሰ ባል ከበደ መሐመድ፣ ራሷ ማሪቱ ለገሰ፣ ዘነበች እሸቴ፣ ዳምጤ መኮንን፣ አሁን ከእኔ ጋር ያሉት ጋሽ አራጌና መሀመድ ከመከም---- ብቻ ብዙ ነበርን፤ አብዛኞቹ አለቁ እንጂ (በትካዜ አንገቷን ደፋች)
እንግዲህ ለ22 ዓመታት ማሲንቆሽን ሰቅለሽ ነበር እና እንደገና ወደ ስራው ስትመለሽ ማሲንቆ መጫወቱ አልጠፋብሽም?
ያን ያህል አላደገናገረኝም፡፡ ትንሽ መደናገር ቢኖርም በአጭር ልምምድ ነው ያስተካከልኩት፡፡ ግን ብዙ ጠፍቶብኝ ነበር ማለት አልችልም፡፡ ለምን? ከልጅነት እስከ እውቀት አብሮኝ ያደገ ነው ማሲንቆ።
አንዳንዶች ማሲንቆ እየተጫወቱ ድምፃዊነቱንም ያቀናጃሉ፡፡ አንቺስ ከማሲንቆሽ ውጭ ድምጽና ውዝዋዜ ትሞክሪያለሽ?
በፍፁም! ምንም ነገር ከማሲንቆ ውጭ አልሞክርም፤ በማሲንቆው ግን የሚያህለኝ የለም፡፡
አንቺ የመጀመሪያዋ ሴት ማሲንቆ ተጫዋች እንደሆንሽ ይነገራል፡፡ ከአንቺ በኋላ ማሲንቆ የምትጫወት ሴት ታውቂያለሽ?
ሴት ማሲንቆ ተጫዋች እንዲህ በግልጽ የሚታወቅ የለም፤እኔ አላውቅም፡፡ አንቺስ የምታውቂያት ሴት ማሲንቆ ተጫዋች አለች እንዴ?
እኔ እንኳን አላውቅም፡፡ እርግጥ ማሲንቆና ክራርን በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት እንደ አንድ ኮርስ የሚወስዱ ተማሪዎች አሉ፡፡ አንቺ ማሲንቆን በልምድ ነው ያወቅሽው፡፡ ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ድርሰት ሲሰጣቸው ኖታ ያነባሉ፡፡ አንቺ እንዴት ነው ዜማውን በማሲንቆ የምትቃኚው?
እርግጥ ነው እኛ በትምህርት አልታገዝንም፡፡ በእኛ ጊዜ ቴክኖሎጂውም ያን ያህል አልነበረም፡፡ የሆነ ሆኖ እኔ የዜማ ድርሰት ሲሰጠኝ ከማሲንቆዬ ጋር ለማዋሃድ በከፍተኛ ደረጃ ጆሮዬን እጠቀማለሁ፡፡ በማዳመጥ ነው ማሲንቆዬን የምቃኘው፤ ከዚያም ሳልቸገር እሰራዋለሁ አመጣዋለሁ፡፡
አሁን ህይወትሽ እንዴት ነው?
አሁንማ ታሪክ ተቀይሮ ከጓደኞቼ ጋር ተገናኝቼ በጣም ደስተኛ ሆኛለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የቀድሞ ባልደረቦቼ  በህይወት ቢኖሩና አብረን ለዚህ ብንበቃ--- አሁን ያለኝ ደስታ እጥፍ ይሆን ነበር፡፡
አሁን ደሴ ነው የምትኖሪው ፤ደሞዝተኛ ሆነሻል፤ ለመሆኑ ደሞዝሽ ስንት ገባ?
አንድ ሺህ ሰባት መቶ ብር አካባቢ አገኛለሁ፡፡ እኔ ብሩ ሳይሆን ስራ ላይ ሆኜ ከጓደኞቼ ጋር መቀላቀሌ ነው ትልቁ ነገር፤ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለሽ የመጀመሪያ ስራሽን ስታቀርቢና ህዝቡ ሲያይሽ ምን አለ?
እኔ ሰው ይሄን ያህል ያውቀኛል፣ ይሄን ያህል ይወደኛል ብዬ አስቤ አላውቅም፤ ፉጨቱና ጭብጨባው ሌላ ነበር፡፡ በህይወት ያለሁ ሁሉ አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ልክ ደሴ ስገባ “እኛ ሞተሻል ብለን ነበር፤ እንኳን አየንሽ” በማለት ለቅሶና ደስታ በተቀላቀለበት ሁኔታ ነበር ህዝቡ የቀበለኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ህዝቡን ባመሰግን ደስ ይለኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ እኔ ቡድኑ ተመስርቶ ቆይቶ ነው የመጣሁት፤ አብዛኛው የቡድኑ አባላት እዚህ ጐንደር ስራቸውን ሲያቀርቡ አይተሽ ከሆነ በጣም ወጣቶች ናቸው፤ እነሱ አቀባበላቸውና የሰጡኝ አክብሮት፣ አሁንም ስንሰራ የሚሰጡኝ ክብር፣ ከልቤ እንድወዳቸው እንዳከብራቸው አድርጐኛል፤ የቡድኑን ወጣቶች ተባረኩ እደጉ ተመንደጉ እላለሁ፡፡ በጣም ደስተኛ አድርገውኛል፡፡
ስለ ፀጉር ስታይልሽ እናውራ---አንቺ ወሎዬ ነሽ፤ ወሎ የሚታወቀው በሹሩባው ነው፤ “እከሌ እኮ ጆፌዋ ጀርባዋ ላይ ተኝቷል” ይባላል፡፡ አንቺ ከልጅነትሽ ጀምሮ ፓንክ ቁርጥን የመረጥሽበት ምክንያት ምንድን ነው?
ፀጉሬ ከልጅነቴ ጀምሮ እንዳልሽው ፓንክ ነው፡፡ ለእናትና አባቴ ብቸኛ ልጅ ነኝ፡፡ ነገር ግን ብዙ ወንድምና እህት ተወልዶልኝ ነበር፡፡ ሁሉም ሞተዋል፡፡ ከዚያ በመጨረሻ ስወለድ ጐስቆልቆል ብዬ እንዳድግ፣ እሰው አይን ውስጥ እንዳልገባ---- በሚል ፀጉሬ እንደተንጨባረረ በወጉ እንዳልሰራ ይደረግ ነበር፡፡ በዚያው ለመደብኝና ፓንክ ሆኜ ቀረሁ፡፡ እንደምታይው ፀጉሬ ጥሩ ነው፤ ሹሩባ ቢሰራ ጥሩ ጆፌ ይወጣል፡፡ (ሳ…ቅ…) ነገር ግን የሆነ ጊዜ ላይ ሹሩባ ለመስራት ሞክሬ ነበር፤ ስሰራ ወዲያውኑ ጭንቅላቴ  ይቆስላል እንጂ ለስታይል ብዬ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ሹሩባ መሰራት ጭራሽ አላስብም፤ ፓንኩን ለምጄዋለሁ፡፡
በድጋሚ ወደ ስራሽ ተመልሰሽ ስላየንሽ ደስ ብሎናል፤ በመጨረሻ ማለት የምትፈልጊው ካለ---
በመጀመሪያ የሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ሰራተኞችን - ጋዜጠኛ ባንቻየሁ አለሙንና ጋዜጠኛ ህይወት ፍሬ ስብሀትን አመሰግናለሁ፡፡ እነሱ አግኝተው በሬዲዮ ድምፄ ባይሰማ በዚያው ወድቄ እቀር ነበር፡፡ በመቀጠል የደቡብ ወሎ ባህልና ቱሪዝም መምሪያን አመሰግናለሁ፤ ወዲያውኑ ፈጣን ምላሽ ነው የሰጡኝ፡፡ በሬዲዮ እንደሰሙኝ ነው ፈልገው ያገኙኝ፣ አቀባበል ያደረገልኝን ህዝብና አድናቂዎቼን፤ አዲስ አድማስንም በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የሙያ አጋሮቼንም እንዲሁ፡፡ በጣም እግዜር ይስጥልኝ፤ባለኝ ቀሪ ዘመኔ በደንብ ለማገልገል እኔም በዚህ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ፡፡  

Published in ጥበብ

         “ተዋነይ ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና ከቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት እና ሊቃውንት” በሚል ርእስ በአቶ ኤፍሬም ሥዩም ተሰማ ተዘጋጅቶ እና በአቶ በላይ መኰንን የአርትኦት ሥራ ተሠርቶ በታተመው የቅኔ መጽሐፍ ላይ ስሕተት ናቸው ብዬ ያመንኩባቸውን አንዳንድ ነጥቦች አንሥቼ፣ ታኅሳስ 19 ቀን 2006 ዓ.ም በዚሁ ጋዜጣ ላይ አስተያየት መጻፌ ይታወሳል፡፡
በሒስ መልክ ያቀረብኩት ጽሑፍ ነቢዩ ዳዊት “ምክር ሠናይት ለኩሉ ዘይገብራ” (መ፡109) እንደሚለው ለመመካከር፣ ለመማማርና ለመተራረም እንዲረዳ ታስቦ የቀረበ ቢሆንም አቶ ኤፍሬም ሥዩምና ሊቀ ኅሩያን ዘደብረ መዊዕ         (ጥር 3 ቀን 2006 ዓ.ም በዚሁ ጋዜጣ የወጣው ጽሑፍ “ከሊቀ ኅሩያን ዘደብረመዊዕ ስለሚል”ነው።) መሆን የነበረበት ግን ሊቀ ኅሩያን እገሌ ዘደብረ መዊዕ ነው፡፡ ጸሐፊው በጋዜጣው ላይ ስማቸውን ለመጻፍ ባይደፍሩም ያው አቶ በላይ መኮንን ናቸው፤ ሁለቱም ሰዎች ሐሳቤን ያልተቀበሉት መሆናቸውን ታኅሣሥ 26 ቀን 2006 ዓ.ም እና ጥር 3 ቀን 2006 ዓ.ም በየተራ ከጻፉት ጽሑፍ ለመረዳት ችያለሁ፡፡
ሁለቱንም ጋዜጦች (እትሞች) ከባሕርዳር እስከ ገረገራ ጊዮርጊስ ድረስ አምጥቶ የሰጠኝ ጓደኛዬ ነው፡፡ ከዋሸራ እስከ ገረገራ ደግሞ 20 ኪሎ ሜትር የሆነ የመኪና መንገድ በመሠራት ላይ ቢሆንም መኪና እንደልብ ስለማይገኝ፣ ከዋሸራ ተነሥቼና በአቋራጭ መንገድ የዘማን ወንዝና ጨረቻ፣ የገረገራ ኢየሱስን ዳገትና ሜዳ በእግር ጉዞ አልፌ ገረገራ ጊዮርጊስ (ዋናው የባሕርዳር ሞጣ መንገድ ያለበት) የደረስኩት በብዙ ድካም ነው፡፡ መልሱ የዘገየብኝም በዚሁ ምክንያት መሆኑን ለአንባቢዎቼ እገልጻለሁ፡፡
እናም የእኔ የሒስ መሠረተሐሳቦች በአምስት ክፍሎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ እነርሱም 1ኛ በተዋነይ ስም በታተመ መጽሐፍ ላይ የተዋነይ ታሪክ በመጠኑም ቢሆን መጠቀስ ነበረበት (በመጽሐፉ ላይ አልተጠቀሰም)፡፡ 2ኛ/ የቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታትና ሊቃውንት ቅኔዎች ተብሎና ከየቅኔ መጻሕፍቱ ተለቃቅሞ በታተመው መጽሐፍ ላይ የነገሥታት ቅኔዎች (ከአፄ እስክንድር ቅኔ በስተቀር) የለበትም፡፡ ይህም ቅኔ ዓፄ እስክንድር ከደቀ እስጢፉ (በስሕተት ተዋነይ ያልኩትን ሊቀ ጥሩያን ዘደብረ መዊዕ ስለአረሙኝ አመሰግናለሁ) ጋር የተዘራረፉት ሥላሴ ቅኔ ነው (የጋዜጣው ዓምድ የሚፈቅድ ከሆነ ወደፊት ስለተዋነይና ደቀ እስጢፋ የምመለስበት (የምጽፍበት) ይሆናል፡፡ ስለሁለቱ ባለ ቅኔዎች ተዋነይና ደቀ እስጢፋ የደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ማርያም የቅኔ መምህር ጥዑመ ልሳን ልየው፣ የጐንጂ ደብረ ጥበብ ቅ/ቴዎድሮስ የቅኔ መምህር ሃይማኖት አድማሱና የደብረ ወርቁ የቅኔ መምህር የኔታ ከብካብ ዓለማየሁ የሰጡትን አስተያየትም የምጨምርበት ይሆናል፡፡
3ኛ. ስለቅኔዎቹ ፍልስፍና የተነገረን ነገር የለም። እነዚህ ከተለያዩ መጻሕፍት የተቀነጫጨቡት ቅኔዎች (አቶ ኤፍሬም ከየገዳማቱና አድባራቱ አዳዲስ ቅኔዎችን አሰባስበህ ብትተረጉም ኖሮ አደንቅህ ነበር) በአቶ በላይ አርታኢነትና በአቶ ኤፍሬም ተርጓሚነት ሲተረጐሙ እንደባህላችን ፍቺ ሰም ወርቅ (ርቀት) ተብለው አልቀረቡም፡፡ በውርስ ትርጉም ሰበብ፣ ምሥጢራቸው ቀርቷል፡፡ ይትበሃሉ ተፋልሷል። አብዛኞቹ ቅኔያቱም የሚታወቁና ቀደም ሲል ታትመው በተለያዩ ሊቃውንት የተተረጐሙ ናቸው እንጂ አዲስ ነገር አልቀረበም፡፡
4ኛ. ቅኔዎቹ ያለ ይትበሃላቸው በአንድ ገጽ ላይ አንድ ቅኔ፣ በሌላ ገጽ ደግሞ ትርጉማቸው (ግጥም)  ለምን ቀረበ? የሌጣ ወረቀት ጋጋታው ለምን ይጠቅማል? በአንድ ገጽ ሁለት ሦስት አራት ቅኔዎች ለምን አልታተሙም?
5ኛ. የብሉይ ዘመን ሊቃውንት የሚባሉት እነማን ናቸው? እነ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬና ሌሎች የተጠቀሱት የብሉይ ዘመን ሊቃውንት ናቸው ወይ? ለምን መለኪያ አልተቀመጠም የሚሉ ናቸው፡፡
ከላይ ለቀረቡት አስተያየቶች አቶ ኤፍሬም የሰጠኝ መልስ መጽሐፉን በወፍ በረር ብቻ እንዳነበብኩት፣ ላቀረብኩት ነገር ምክንያት እንደሌለኝ፣ ለማረም ሳይሆን ለማማረር፣ ለማስገንዘብ ሳይሆን ለመሳደብ፣ ፀሐይ የሞቃቸውን አገር ያወቃቸውን ታላቁን ሊቅ (አቶ በላይን ማለቱ ነው) ከክፉ ቅናትና ከግል ቂም ተነሣሥቼ (ገጽ 24 እና 26 ይመለከቷል) እንደተሳደብኩ እና በዚሁ ድርጊቴ ምሁር አይሉኝ መሀይም የማልረባና ከንቱ ሰው እንደሆንኩ ነው። ነገር ግን አቶ ኤፍሬም ልንገርህ አይደል! በአንተና በአቶ ዘደብረ መዋዕ ዕውቀትና በተፈታች ሚስት የሚቀና ቢኖር ጅል ሰው ብቻ ነው፡፡
አቶ ኤፍሬም በአስተያየቴ ታላቁ ገጣሚና ባለቅኔ ኤፍሬም ባለማለቴና ይልቁንም “አቶ” በሚለው የወል ማዕርግ ስለጠራሁህ የተበሳጨህብኝ መሆኑን ከጽሑፉ ተረድቻለሁ፡፡ በተመሳሳይም የቅኔ ዕውቀቱ ሳይኖረኝ ከመሬት ተነሥቼ አፌን እንደከፈትኩብህ ገልጸሃል፡፡ እኔ ግን ብዕር ነበር የከፈትኩብህ የመሰለኝ፡፡ ለካ አፌንም ከፍቸዋለሁ አያ?
በአጠቃላይም በራስህ ግምት ንብና ተርብ የሆንከውንና የማይነካውን ባለቅኔ በመንካቴ “ኩት አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ” ብሎ ሰነፉ “ሊቅ” ሐሳቤን ሳይቀበለው አልፏል፡፡ አቶ ኤፍሬም ሌላው ሌላው ነገር ይቅርና በመጀመሪያ አንተ ይህንን መጽሐፍ አዘጋጅተህ በማቅረብህና የቅኔ መጻሕፍትን ቁጥር ለማባዛት ጥረት በማድረግህ የማላከብርህ ለሥራህም ዋጋ የማልሰጠው እንዳይመስልህ፡፡ ሰው የሚያውቀውን ነገር በለጋስነት ለሕዝብ በማቅረቡ ቸርና ድንቅ ሰው ተብሎ መታየት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ አንተ ንፉግ አይደለህም፡፡
እኔም አስተያየት ስሰጥህ ከቅንነት በመነሣት ነው፡፡ ዝም ማለት‘ኮ እችላለሁ፡፡ ወይም ይበል ይበል ማለፊያ ነው ብዬ ማለፉ አይጠፋኝም። በሒስ በመረዳዳት በመተጋገዝ መሥራት እንጂ መናናቅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምናልባትም አቶ ኤፍሬም ስለቅኔ ስትተረጉም ፀሐይ ከሞቀው አገር ከአወቀው ሊቅ ጋር ስለዋልክ ወርቁ ይጠፋሃል ብዬ ስለአልገመትሁ አንተ እንዳልከው ብዙ ማሳያ ምሳሌዎችን አላቀረብኩም፡፡ በዚህ ትክክል ብለሃል።
ለአብነት በመጽሐፉ ገጽ 64 ላይ የሠፈረውን ዘአምላኪየ ቅኔ እንመልከት፡፡ ቅኔው በዕለተ ደብረታቦር የቀረበ ነው፡፡ ዕለቱ የመለኮት ግርማ ሞገስ (ብርሃኑ) በታቦር ተራራ ላይ ለሙሴ፣ ለኤልያስ፣ ለጴጥሮስና ለሌሎች የታየበት ነው። ነቢያትና ሐዋርያቱ የመለኮቱን ብርሃናማ ግርማ ለማየት ስለአልቻሉ መሬት ላይ ወድቀዋል፤ ወደነበሩበትም ተመልሰዋል፡፡
ባለቅኔው ሙሴን “በታቦር ያየኸው ደመና በፊት እንደምታውቀው መና ሳይሆን ከመሬት የሚቀላቅለው የመለኮት ግርማ፣ በዓይን ለማየት የማይቻለው ብርሃን ነው” ማለታቸው ነው፡፡ ሌላም ምሳሌ ላቅርብ፡፡ (ምሳሌው ጉባዔ ቃና ነው)
“ጠየቆ ደቅስዮስ ለደቅስዮስ ምክንያተ ደቅስዮስ ከንቶ፣
ብእሲቱ መንበር ከመ በይነ ምንት ጸልአቶ”
ፍቺ “ደቅስዮስ ደቅስዮስን የደቅስዮስ ምክንያት ምንድነው? ብሎ ጠየቀው” (መንበር ባለቤቱ ስለምን እንደጠላችው ጠየቀው)
ሰም - አንድ ጐልማሳ ባለቤቱ ስትጠላው፣ ጓደኛው ምነው በምን ምክንያት ጠላችህ? ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
ወርቅ - (ርቀት) ደጉ፣ ትሑቱ ደቅስዮስ ይቀመጥበት በነበረው ወንበር ላይ ተንኮለኛው ቀናተኛው ደቅስዮስ ሲቀመጥበት ወንበሩ ገለበጠችው፣ ፈነገለችው ማለት ነው፡፡ (ይህ ታሪክ ታኅሣሥ 22 ቀን በሚነበበው ተአምረ ማርያም ላይ ይገኛል)
እኔ ከአቶ ኤፍሬም የቅኔ ስብስብ እጠብቅ የነበረው እንደዚህ ዓይነቱን መንገድ ተከትሎ እንዲተረጉመው (እንዲገጥመው) ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ የምንነጋገረው ስለ ቅኔ ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ በታተሙ የቅኔ መጻሕፍት ገጾች ላይ ቅኔዎቹ በአንድ ገጽ ላይ ሁለት ሦስት አራት እየሆኑ ነው የቀረቡት፡፡  
ለዚህ ማስረጃ እንዲሆን የብላቴን (ጌታኅሩይን፣ የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን፣ የይኩኖ አምላክ ገብረ ሥላሴን፣ የይኄይስ ወርቄንና የሌሎችን መጻሕፍተ ቅኔ መመልከት ይቻላል፡፡ በአንተና በአቶ በላይ እምነት ግን ይህንን የተዋችሁት ለሥነ ውበት ስትሉ ነው፡፡ እና ውጤቱ “እውር ለእውር የትማርሑ፣ ወይወድቁ ውሰተ ግብ” ሆነ፡፡
በተረፈ ጥበቡ ገሜ ደርሶ በሚያገሳና በሚታበይ አንድ ዲያቆን ላይ የተቀኙትን ፍርንዱስ ቅኔ (አማርኛና ግዕዝ) ወደ አማርኛ ቀይረኸው በማየቴ “አቤት ይኸ ሰው ለካ ታላቅ ፈላስፋ ነው ብዬ ተደመምኩብህ፡፡  ጥበቡ አባሐጋር ለእመት ገላነሽ ሐዲስ የላኩላቸው ዕንቆቅልሽ ቅኔ አላቸውና መቼም ለአንተ “እስመ አልቦ ነገር ዚይሰአኖ ለኤፍሬም” ነውና እንድትፈታላቸው እጋብዝሃለሁ፡፡
“ሞቶን ሞተኪ ሞተ ፈጣሪ፤ ፈጣሪ፣
እመይቴ ገላነሽ ይህንን ፈትተሽ ፈክሪ፡፡”
የራሴንም አንድ ዘአምላኪየ ላክልልህ፡፡
“ለዘለዘሔር ደቅስዮስ መጸብሐ ሙሴ ዐመፆ፣
ደቅስዮስ መጸብሐ ሙሴ መገስጽ ገሰጸ፡፡
ወዘለዘለሔር ብልጣሶር ትስትማና ክብሩ ሐወጸ፡፡” የቤት ሥራ ይሁንህ!
የአቶ በላይ መኰንን አቀራረብ ደግሞ የሚከተለው ነው፡፡ በመጀመሪያ አቶ ዘደብረመዋዕ እና አቶ ኤፍሬም ለስሜ (ጵርስፎራ) መተርጉማን ሆነው ለማብራራት ተፍጨርጭረዋል፡፡ ስም‘ኮ መጠሪያ ነው፡፡
መተርጐም አስፈላጊው አይደለም። አቶ በላይ ስሙን በጋዜጣው ላይ ለመጻፍ ስለፈራ ሊቀመኅሩያን ዘደብረ መዊዕ ብሎ ይጀምራል፤ ማዕርግ የሚመጣው‘ኮ ከስም ጋር ነበር፡፡ ማዕርጉ በአየር ላይ ተንጠልጥሎ ቀረሳ! አቶ በላይ ስለእኔ ሰብእና (ማንነት) ለማወቅ ብዙ ጥሯል፤ ተጨንቋል። የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ልሳን፣ የቅኔ ዕውቀት ያለው ሰው ይሆን? ብሎ ሲጠበብ ከቆየ በኋላ፣ ከዘመናዊው ጥበብ ጋር ያልተዋወቅሁ ሰው መሆኔን ደርሶበታል፡፡ (በስለላ ወይንም በጥንቆላ) ሊሆን ይችላል፡፡
“በኢትዮጵያ እንደአሸን ከሞሉትና እንደ አበባ ከፈኩት ጥበባት ውስጥ አንዱና በሌላው ዓለም የሌለው የግዕዝ ቅኔ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡” የሚለውን አገላለጼን በመቀንጨብ የእኔ የቅኔ ዕውቀት ብዥታ ከዚህ እንደሚጀምር ለመፈላሰፍና ለደላገጥ ሞክሯል፡፡
በተለይ የአቶ ዘደብረ መዋዕ (በአገሬ አጠራር ደብረ መይ ደብረማይ) አጻጻፍ ከአቶ ኤፍሬም የሚለየው መሠሪ በሆነ ደብተራዊ አካሄድ ከብዙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር ለማነካካት መፍጨርጨሩ ነው፡፡ አቶ በላይ እኔ የገጠምኩት ከአንተ ሐሳብ ጋር እንጂ ከአንተ ጋር አይደለም፡፡ የምናወራው የምንነጋገረው ስለግዕዝ ቅኔና በመጽሐፍ መልክ ሲታተም ምን መደረግ እንዳለበት ነው፡፡ አንተ ደግሞ የምትደሰኩረው የአማርኛ ሥነግጥም መጻሕፍትን የአጻጻፍ ስልት ስለአለመገንዘቤ ነው፡፡
አቶ በላይ ለመሆኑ የአንድ ርእሰ ጉዳይን ጭብጥ አታውቅም እንዴ? ለምን እዚያም እዚያም ትረግጣለህ? አሁንም የምናወራው ስለ ቅኔያት አተረጓጐምና በመጽሐፍ መልክም ሲታተሙ በአንድ ገጽ ላይ ሁለት ሦስት አራት እየሆኑ እንዴት እንደሚቀመጡ ነው እንጂ ከተራ ቁጥር 1-5 (ከሰሎሞን ዴሬሳ እስከ ሜሮን ጌትነት) እንደዘረዘርከው የአማርኛ ድርሰቶች አይደለም፡፡
አቶ በላይ ተመራምረህ እንደደረስክበት አበባው መላኩ,፣ እንዳለጌታ ከበደ,፣ ሜሮን ጌትነትና አያልነህ ሙላቱ “ባለ ቅኔዎች” መሆናቸውን አላውቅም ነበር። ለማንኛውም እኔ የማወራው ስለ ቅኔ ነው፡፡
የቅኔ ሥራዎች ሁለት ሦስት ዐራት እየሆኑ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ በመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ፣ በአለቃ ይኩኖ አምላክ ገብረሥላሴ፣ በነ ይኄይስ ወርቄ,፣ በነቀሲስ ከፍያለው መራሒ… የቅኔ መጻሕፍት ላይ እንዴት እንደተጻፉ እንድታዩ ደግሜ አሳስባችኋለሁ፡፡
አቶ በላይ “የቅኔ ተማሪ ነበርኩ” ካልክ የቅኔ መምህራን በራሳቸው፣ በጓደኞቻቸው፣ በቤተሰባቸው፣ የዕቡይነትና የአላዋቂነት፣ የስንፍናና የዳተኝነት፣ የአሉባልተኝነት ባሕርይ በአለው ዲያቆን፣ ቄስ፣ ምዕመን፣ ደብተራ ላይ ቅኔ እንደሚቀኙ የታወቀ ነው፡፡
ቅኔው ደግሞ ተናድደው እንዲማሩ እንዲታረሙ እንዲሠልጡ ለማድረግ ነው እንጂ ሰብእናቸውን ለመንካት አይደለም፡፡ መምህር ጥበቡ አባ አጋር ዘቦገና ግራር በዘመናቸው መወድስ ቅኔ የተቀኙት አልታዘዛቸው፣ አላከብራቸው እያለ ለአስቸገራቸውና ደርሶ ለሚያገሳው፣ ለሚታበየው አንድ ዲያቆን እንጂ ለዲያቆናት ሁሉ አይደለም፡፡ የእኔም አገላለጽ ይህንኑ መሠረት ያደረገ ነው እንጂ የአንተን የአንድምታ (እንዲህ ማለቱ ነው የሚለውን ቧልት) ትርጓሜ የሚከተል አይደለም፡፡
በቅንነት ለተልእኮ ምሥጢር የሚፋጠኑትን፣ በክቡር ሥጋውና ደሙ አማካይነት ምዕመናትንና ምዕመናንን ከክርስቶስ ጋር የሚያገናኙትን አባቶችና ወንድሞች አይመለከትም፡፡ ልክ እንደ ጥበቡ አባ አጋር ሁሉ በራሳቸው የሕይወት ታሪክና አኗኗር ላይ ተመሥርተው ማዕበል ደሴና ዕቡይ ካሳ (ዘጐንጵ) ያሬድ ዘመንግሥቶ፣ እመት ገላነሽ ዘጽላሎና ሌሎች የተቀኙዋቸው ቅኔዎች በርካታዎች ናቸው፡፡
ለአስረጅ ያህልም አንዱን አቀርባለሁ፡፡ አንድ ወቅት ማዕበል ደሴ በሌሊት ሲሄዱ ሽፍታ በመንገድ ላይ አገኛቸውና ተኩሶ እጃቸውን መትቷቸው ነበር፤ እናም  ከመኖሪያ ቤታቸው እስኪደርሱ ድረስ ደማቸው ብዙ ፈስሷል፡፡ ይህንኑ አስተመልክተው በራሳቸው ላይ የሚከተለውን መወድስ ዘርፈዋል፡፡
መወድስ ዘማዕበል ደሴ
ለመራር እዴየ ማየ ሰማርያ፤ ቀሰማ ለጽዮን ኤልሳዕ ድምፀ ብርት፡፡
አኮኑ ትትናገር ሕፀፀ አካል መንግሥት፡፡
ለብልጣሶር መዝራዕትየ ዘተጽሕፈ በገፀ ፈጣሪ ዳንኤል ሐሜት፡፡
እኩንሂ ጊዜ ምሳሌ ሆሣዕና ጠቢብ ዳዊት፡፡
በዕለተ ዐርብ ቀነውኒ እንዘ የአግቱኒ ከለባት፡፡
ወአመ ተንሣእኩ አነ እምአፈ መቃብር ጽንእት
ማርያም ተዋርዶ መጽአት በሌሊት፡፡
አያ ዘደብረመዊዕ ቅኔ በስማ በለው አይታወቅም የሚለውን አባባሌን ወስዶ፣ እንደ ስሕተት ከቆጠረ በኋላ በራሱ አገላለጽ “ይህ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችንና ሰባኪዎችን መናቅ ነው፡፡ እነ ኦገስት ዲልማንና ወልፍ ሌዝላው ዋሸራ፣ ጐንጂና ዋድላ ቅኔ ቤት ገብተው አልተማሩም፡፡ ሥራውን ግን ሠርተውታል” ይለናል፡፡
የሰንበት ተማሪዎችንና ሰባክያነ ወንጌሎችን፣ እነ ዲልማንና ወልፍ ሌዝላውን በእጅጉ የማከብራቸው ናቸው፡፡ በተለይ እነ ዲልማንና ወልፍ ሌዝላው በምርምር ሥራቸው እኛ ያልሠራነውን የሠሩልን ስለሆነ ባከብራቸውም እንዳንተ በስማ በለው ያጠኑ ቅኔ አዋቂዎች ነበሩ፤ ብዬ ግን አላምንም። የምናወራው ስለ ቅኔና ባለቅኔ ነው፡፡ ወንጌል ማጥናት፣ መስበክ፣ የምርምር ሥራ መሥራት ሌሎች ነገሮች ናቸው፡፡ ሁሉም በየሙያቸው የተከበሩ ናቸው፡፡
አያ ሊቀኀሩያን ለመሆኑ ምኑን ከምን ጋር ነው የምታገናኘው? ሁለታችሁ አባትና ልጅ (ዘደብረ መዊዕና ኤፍሬም) ሐሳብ የማትቀበሉ፣ በስህተት አረንቋ ውስጥ ወድቃችሁና ተዘፍቃችሁ፣ እዚያው በዚያው የምትዛቅጡ ድንክየዎች በመሆናችሁ አሳዘናችሁኝ፡፡
አያ ዘደብረ መዊዕ አንዴ “የሥነልሳን ሊቅ”፣ ሌላ ጊዜ “የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ሒስ ባለሙያ፣ ባለቅኔ፣” ሌላ ጊዜ “የድጓ ሊቅ፣” ሌላ ጊዜ ጸሐፊ፣ ደራሲ፣ ገጣሚ ምሉዕ በኩለሔ ነኝ” ትለናለህ፡፡ ሁሉን ነኝ ብለህ ታምናለህ፡፡ የዋሸራ ሰው አለመሆኔን ስለደረስክበት፣ ነገ ደግሞ “የስለላ ባለሙያ ነኝ” እንደምትል እሙን ነው፡፡
እኔ አገር ዋሸራ ደብረ ምዕራፍ ማርያም ገዳም ውስጥ ውቤ የተባለ ሰው አለ፡፡ ውቤ አንድ ቀን ልዩ መንፈስ አነሣሣውና  ደርሶ “ባለቅኔ ነኝ፣ አናፂ ነኝ፣ ግንበኛ ነኝ፣ ቀለም ቀቢ ነኝ፣ መነኩሴ ነኝ፣ ሊቀሊቃውንት፣ ዐርበኛም ነኝ” ይል ጀመር። እንዲያው ብቻ “በምድር ላይ ላለው ዕውቀት ሁሉ ባለቤቱ እኔ ብቻ ነኝ” አለ፡፡ ከዚያ ሁኔታውን የታዘበችው እናቱ “ውቤ በምድር ላይ ሁሉንም ነገር አዳረስከው፤ አሁን የቀረህ የሰማዩ ብቻ ነው” አለችው፡፡ ዘደብረ መዊዕም ሌላው ውቤ ሆንክብኝ።
አያ ዘደብረ መዊዕ “አንድ ያላት እንቅልፍ የላት” እንዲሉ ስላሳተምካት “ሕያው ልሳን” ብዙ ነግረኸናል፡፡ መቼም ግስ ከነጓዙ የተፈጠረው ዋሸራ መሆኑን ሳትሰማ አትቀርም፡፡ ፈጣሪውም ተክሌ ዘዋሸራ ናቸው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ግስና መዝገበቃላትን ያለዋሸራ ማርያም ገዳም ፈቃድ እንደፈለጉ ስለሚያሳትሙ፣ የኔታ ጥዑመ ልሳን ልየው የሚከተለውን ጉባኤ ቃና እንደተቀኙ ልንገርህ፡፡
“ኢታምልክ ግስ አምላከ ሕሳዌ መቅለሌ፤
እንዘ ፈጣሪከ ፈጣሪከ ተክሌ፡፡”
ትርጉም - ግስ ቀላል የሆነውን የውሸት አምላክ አታምልክ፤ ፈጣሪህ ተክሌ ነውና፡፡
በአሁኑ ጊዜም “ግስ ዘዋሸራ” በገዳሟ ሊቃውንት በመዘጋጀት ላይ ሲሆን ሲታተም አያ ዘደብረመዋዕ ለምን እኔ ሳላውቅ ታተመ ብለህ አራስ ነበር እንደምትሆን እገምታለሁ፡፡
ሌላው ያስገረመኝ ደግሞ ዋሸሬ እንዳልሆንኩና አዲስ አበባ ውስጥ መሽጌ እንደ ጻፍኩብህ፣ ከዋሸራ ሊቃውንት ተርታ እንደማልመደብ… አስበህ የዋሸራን ሊቃውንት ስም መቁጠርህ ነው፡፡ እኔኮ የፈለግሁት ቅኔ እንድትቆጥር ነው እንጂ የሊቃውንቱን ስም እንድትደረድር አይደለም፡፡ ለመሆኑ እኔ ገና ከጅምሩ የዋሸራ ሊቅ ነኝ ብዬ ጽፌያለሁ እንዴ? ከየት አመጣኸው? አዲስ አበባ ልመሸግ ዋሸራ፣ ባድመ ልመሸግ ጐርጐራ፣ ወላይታ ልመሸግ አሳይታ …ጉዳያችን አይመስለኝም፡፡
እኒያ ጳጳስ (ብፁዕ አቡነ በርናባስ)  ነፍሳቸውን ይማረውና የታላቁን ባለቅኔ የሊቀ ኅሩያን ዘገየን የሙያ ስም በአንተ አገላለጽ “በአሁኑ ጊዜ ለእንቶ ፈንቶው ሁሉ ይሰጣልኮ” ብለው ሲሰጡህ ነገሩ ሁሉ የተበላሸብህ ይመስለኛል፡፡ አልፈልግም ብለህ ቢቀርብህ ኖሮ እየታበይህ  ዛሬ ከብዙ ስህተት ላይ አትወድቅም ነበር፡፡
ከአንተ ጋርም ሆነ ከኤፍሬም ጋር ጥላቻ፣ የጥቅም ግጭትና ቅራኔ የለኝም፡፡ አታውቁኝም፤ አላውቃችሁም፤ ያገናኘችን ይህቺ መጽሐፍ ናት፡፡ እምነቴን መሠረት አድርጌ አስተያየት ብጽፍ ባክ ባክ አላችሁኝ፡፡ እና እናንተ ሃሳብ የማትቀበሉ አብዳን (ሰነፎች) ናችሁ ብየ ትቻችኋለሁ፡፡ በሌላ አገላለጽም በብረት አጥር ውስጥ ተዘግታችሁ የምትኖሩ ጽልመታውያን ናችሁ፡፡
አንባቢዎቼንም በ እቡይ ካሳ ቅኔ እሰናበታለሁ፡፡
እቡይ ካሳ በአሉበት ማንም ሰው ቅኔ አይቀኝም ነበር፡፡ እኒህ ሊቅ ደብረወርቅ ማርያምን ከልባቸው ያፈቅሩዋት ስለነበር፣ አንድ ቀን የኤዎስጣቴዎስን ክብረ በዓል ለማክበር ወደዚያው ይሔዳሉ፡፡ የደብረወርቅ ሊቃውንት ደግሞ ቅኔ በተለይ መወድስ ለእንግዳ ስለማይሰጡ በራሳቸው ተማምነው ተቀምጠዋል፡፡ በድንገት ግን ከቅኔ ማኅሌቱ አለፍ ብሎ ዕቡይ ካሳን ሲያዩዋቸው ሐሳባቸወን ቀይረው “ኧረ እናንተ ከጐንጂ የመጡ ትልቅ እንግዳ እዚያ ቆመዋል” ይላሉ፡፡ ደብረወርቆች
ተደናግጠው ከመኻላቸው ያቆሙዋቸዋል፡፡ መወድሱንም ይሰጡዋቸዋል፡፡
መወድስ (ዘዕቡይ ካሳ)
አስተቃርቦተ ሕዝብ ቤተ ምስለ ቤተሕዝብ፤ ለእንተ ይኤዝዝ ቃለ ኅሰተ  ኢሳይያስ ኮነ
እመ አሐቲ ዘኮነት ቤተ ማዕቀበ ወልድ ቤትነ፡፡
ኢኮነ ነግደ ወፈላሴ ቅዱሳን በሀገርክሙ ደብረወርቅ ንሕነ፡፡
ነገረ መሠረት አመ ተወጥነ፣
እስመ ሰብአ ቤቱ ለሔር ኤዎስጣቴዎስ ኩልነ፡፡
ለዓለም ደብረወርቅኒ ደብረ ምሥጢር እመት ትሰመይ ልሳነ፡፡
አልቦ በደብረወርቅ ወርቀ እግዚኡ ዘደፈነ፡፡
እስመ ዘንትቃወም ሕዝብ በዓውደ አፍቅሮ ምናነ፡፡
ጥበብ ደብረወርቅ በመንኖ ምሥጢር ጸድቀተነ
እናም ዕቡይ ይሄንን ቅኔ ከተቀኙ በኋላ በደብረወርቅ ካህናት ዘንድ በእጅጉ ተደንቀውና ካባ ላንቃ ተሸልመው ወደ ሀገራቸው ጐንጂ እንደተመለሱ ይነገራል፡፡ እና እኒህን ዕቡይ በጥበበኛነታቸው የማያደንቅ ማን አለ? ጥበበኛና አዋቂ ሳይሆን የሚታበየውን ግን ማንም አያከብረውም፡፡
እና ኤፍሬምም ከዚህ በፊት ያልተተረጐሙና አዳዲስ የሆኑ ቅኔዎችን ከየገዳማቱና አድባራቱ አስሰህ በማምጣት ብትተረጉምልን ኖሮ ማለፊያ ነበር፡፡ ስሕተት ውስጥ የከተተህም አያ ዘደብረመዊዕ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ የማይሆን አማካሪ (ጠበቃ) ያስረታልና፡፡     

Published in ጥበብ
Monday, 10 February 2014 07:48

የቫለንታይን ቀን

        ሉሲ ጭንቅላቷን መስተዋቱ መስኮት ላይ አስደግፋ ያሸለበች ትመስላለች፡፡ ባቡሩ በተንገራገጨ ቁጥር   ከመስኮቱ ጋር ትላጋለች። በተደጋጋሚ ከተላጋች በኋላ ዓይኗን ገልጣ ዙሪያዋን መቃኘት ያዘች፡፡ ባቡሩን የሞሉት ጥንዶች ናቸው፤ፍቅረኛሞች፡፡ ዓይኗን መልሳ ጨፈነች- ጥንዶቹን  ላለማየት፡፡
በየመሃሉ ባቡሩ ያቃስታል፡፡ የድካም ድምጽ፣ የመታከት እንጉርጉሮ ያስተጋባል፡፡ የእሷና የባቡሩ ህይወት በሆነ መንገድ የሚመሳሰል ሆኖ ተሰማት፡፡ ባቡሩ ቀኑን ሙሉ በአንድ መስመር ሲጓዝ ይውላል። በአንድ አቅጣጫ ሲመላለስ፡፡ በራሱ ፍጥነት የመጓዝ ነፃነቱን ተነፍጓል፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች ይከንፍና በርዶ ይቆማል፡፡ እንደገና ደግሞ ይነሳል፡፡ ጉዞ ይጀምራል፡፡ መቆም … መነሳት፡፡ የሚፈቀድለት ይሄ ብቻ ነው፡፡
  ባቡሩ ሲንገራገጭ ሉሲ ዓይኗን ገለጠች፡፡ አንድ ወንድና ሴት ከባቡሩ ለመውረድ ከመቀመጫቸው ሲነሱ ተመለከተች፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘዋል። ወንድየው ክንዶቹን ፍቅረኛው ትከሻ ላይ አድርጐ ግንባሯን ሳማት፡፡ እሷም እጇን ወገቡ ላይ ጠምጥማ፣ ጣቷን የጂንስ ሱሪው የኋላ ኪስ ውስጥ እየከተተች  ጭንቅላቷን ትከሻው ላይ አሳረፈች፡፡ በርቀት ሲታዩ በአንድ ላይ የተሰፉ ይመስላሉ፡፡ ለእነሱ ብቻ ጊዜ መቁጠሩን አቁሟል፡፡
 ከእነሱ አጠገብ አንድ ዘናጭ ወጣት ቆሟል - በእጁ ቀይ አበቦች የያዘ፡፡ እየተቁነጠነጠ አስሬ ሰዓቱን ይመለከታል፡፡ ይሄኔ አንዲት ወጣት  ቆማ እየጠበቀችው እንደሆነ ሉሲ አሰበች፡፡ እሷም እንደሱ አስሬ ሰዓቷን እያየች፡፡
“ሂድ” አለችው፤ ባቡሩን - ጮክ ብላ፣ ግን ድምፅ ሳይሰማ፡፡ ሉሲ ተጨማሪ የፍቅር ትዕይንቶችን ማሰብም ሆነ ማየት አልፈለገችም፡፡
ባቡሩ ሃሣቧን የተረዳ ይመስል በሩ በቀስታ ተንሻትቶ ተዘጋና መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ቢያንስ ለጥቂት ደቂቃዎች እንደማይቆም አውቆ በደስታ ይከንፍ ጀመር፡፡ ሉሲ የውጭውን ትዕይንት ስትመለከት በፈገግታ ተሞላች፡፡ አረንጔዴው፣ አመድማው፣ ገብስማው----- ሁሉም ትዕይንት ከባቡሩ ፍጥነት ጋር ብዥ እያለ ያልፋል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ባቡሩ እንጉርጉሮ አሰማ፡፡ ማልቀሱ ነበር - ለምን በረድኩ፣ ለምን ተገታሁ ብሎ፡፡ እየቆሙ መነሳቱ የታከተው ይመስላል፡፡ በሩ በዝግታ፣ በድካም ስሜት ተንሻትቶ ተከፈተ፡፡ ሌሎች ጥንዶች ደሞ ተሳፈሩ፡፡
ሰውየው ከሉሲ አጠገብ፣ ሴቲቱ ፊት ለፊቱ  ተቀመጠች፡፡ በዕድሜ የሉሲ እኩያ ትሆናለች። ከፍቅረኛዋ በቀር ሌላ ነገር አታይም፡፡ ዓይኗቿ እንደክዋክብት ያበራሉ፡፡ ፍቅረኛዋ ጠጋ ብሎ ከንፈሯ ላይ ሳማትና ጠቀስ አደረጋት፡፡ ይሄኔ ፊቷ የበለጠ ፈካ፡፡ በስር በኩል ጉልበታቸው ተነካክቷል። በላይ እየተሳሳቁ ይደባበሳሉ፡፡ ሉሲ ዓይኗን ጨፍና  ሃሳቧ ውስጥ ተጠቀለለች፡፡
ድንገት አይኗን ስትገልጥ መውረጃዋ ደርሷል። ገና ባቡሩ ፍጥነቱን ሳያበርድ ከመቀመጫዋ ዘላ ተነሳች። “አመሰግናለሁ፤ የነገ ሰው ይበለን” አለች ለባቡሩ - በለሆሳስ፡፡ ከየካቲቱ የሚጋረፍ ቀዝቃዛ አየር ራሷን ለመከላከል ካፖርቷን እስከላይ ድረስ እየቆለፈች ከባቡሩ ወረደች፡፡ እንደ ጩቤ የሚዋጋው ብርድ ነበር የተቀበላት፡፡ ሁለት እጆቿን ካፖርት ኪሶቿ ውስጥ ከትታ  መገስገሷን  ቀጠለች - ወደ ሥራዋ። ሉሲ ዱብሊን ከተማ እምብርት ላይ በሚገኝ አንድ የፈረንሳይ ሬስቶራንት ውስጥ አስተናጋጅ ናት።  
ቀኑ ፌብሯሪ 14 ነው፤ ቫለንታይንስ ዴይ!
በዚህ ምሽት የእነሉሲ ሬስቶራንት ገበያው እንደ ጉድ ይደራል፡፡ እንግዶች ጠረጴዛ “ሪሰርቭ” የሚያደርጉት ከሳምንት በፊት ነው፡፡ አስተናጋጆች “የፍቅረኞች ቀን” በመጣ ቁጥር ማታ የሚመደበው ማነው በሚለው ጉዳይ መጨቃጨቃቸው የማይቀር ነው፡፡ ሁሉም ምሽቱን ከፍቅረኛው ጋር ማሳለፍ ይፈልጋል፡፡ እዚህ ውስጥ የሌለችበት ሉሲ ብቻ ናት፡፡ ቫለንታይንስ ዴይ እሷን አይመለከታትም። ለዓመላቸው ያህል ይጨቃጨቃሉ እንጂ በቫለንታይን ምሽት ሥራውን የሚሸፍነው ማን እንደሆነ አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ለነገሩ ሉሲ ሁሌም የማታ ምድብ ናት፡፡ በተለይ የፍቅረኞች ቀን የሚከበርበት ምሽት ሲሆን ዋና ባለዕዳ እሷ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ግን ወድዳና ፈቅዳ ነው፡፡
ሉሲ በሚቀጥለው ወር 31ኛ ዓመቷን ትይዛለች። ሆኖም ፍቅረኛ ኖሯት አያውቅም፡፡ እንደዚያች ባቡሩ ውስጥ እንዳየቻት ሴት ግንባሯ ላይ የሚስማት ሰው የለም፡፡ የአበባ ስጦታ ተበርክቶላት አያውቅም። ከንፈሯን ለመሳምም አልታደለችም፡፡ ቀጠሮ እንዳያረፍድባት የሚጨነቅላት ወንድ አላገኘችም። ዓይኑን ትክ ብላ ስታየው ቆይታ፣ለዘላለም ከእሱ ጋር ለመኖርና የእሱ ብቻ ለመሆን የተመኘችው ሰው የለም፡፡ የወደፊት ልጇን ስም እንድታስብ ያደረጋት ወንድ አልገጠማትም፡፡ ሉሲ አፍቅራም ተፈቅራም አታውቅም፡፡
ስለ ፍቅር አታውቅም ማለት ግን አይደለም። አሳምራ ታውቃለች፡፡ የፍቅረኞችን ታሪክ በመጽሃፍት አንብባለች፡፡ በባቡር ስትመላለስ ብዙ ፍቅረኞችን አይታለች፡፡ ጓደኞቿ ስለፍቅረኞቻቸው ሲያወሩም ሰምታለች፡፡ ከሚፋቀሩ ወላጆች ጋር ነው ያደገችው፡፡ በፊት በፊት በፍቅር ላይ ያላት እምነት ፅኑ ነበር፡፡ ዕድሜዋ ሲሄድና እያንዳንዱ ዓመት ለእሷ የተጣፈላትን የነፍስ ጓደኛ ሲነፍጋት እምነቷ ተሸረሸረ፡፡ ፍቅር ለሁሉም የተሰጠ ጸጋ ሳይሆን ዕድለኞች ብቻ የሚያጣጥሙት ነው ብላ ተፈጠመች፡፡ ብቸኝነትን ጓደኛዋ አደረገች፡፡
የፖስት ካርድ መሸጫ መደብሮች በወንዶችና በሴቶች ተጨናንቀዋል፡፡ ሁሉም ለፍቅረኛው ስጦታ እየሸመተ ወደቀጠሮው ሥፍራ ለመድረስ ይጣደፋል፡፡ ይሄ ሁሉ ግርግር ግን ለሉሲ ምኗም አይደለም፡፡   በየሱቆቹ መስኮቶች ላይ የተሰቀሉት ቀያይ የልብ ቅርጾች /ምስሎች/ የመንገደኛን ቀልብ ይስባሉ፡፡ ሉሲን ግን አልሳቧትም ፤ ሆድ አስባሷት እንጂ፡፡ እግሯን እየጎተተች ነው ሥራ ቦታዋ የደረሰችው፡፡
ሬስቶራንቱ በር ላይ የቫላንታይን ቀን ልዩ ሜኑ (የምግብ ዝርዝር) ተሰቅሏል፡፡ የምግብ ቤቱ ዙሪያ ገባ  በትላልቅ  ቀያይ የፍቅር  “ልቦች” አሸብርቋል፡፡
12፡30 ላይ የመጀመርያዎቹ የምሽቱ ጥንዶች የሬስቶራንቱን በር ከፍተው ገቡ፡፡ ሉሲ ክፍሉን ብሩህ በሚያደርግ ፈገግታ ተቀበለቻቸው፡፡
“ጤና ይስጥልን፤ እንኳን ደህና መጣችሁ” አለች ደስተኛ ለመምሰል እየሞከረች፡፡
“እናመሰግናለን፤ ለሁለት ሰው ቦታ ትሰጭናለሽ?” ሰውየው ኦናውን ሬስቶራንት እየቃኘ በትህትና ጠየቃት፡፡
“ቀድማችሁ አሲዛችኋል?” ፈገግታ ሳይለያት ጠየቀች፡፡
“አዎ፤ ማክ ግላድዌል በሚል ለ 12፡30 አሲዘን ነበር---”
ሉሲ የእንግዶችን ስም ዝርዝር የያዘውን መዝገብ እየገለጠች ካየች በኋላ     “ትክክል ነው ተይዞላችኋል፤ ካፖርታችሁን ልቀበል----?”
ካፖርታቸውን ተቀብላ ፊት ፊት እየመራች ወደተያዘላቸው ጠረጴዛ ወስዳ አስቀመጠቻቸው። ከዚያም የምግብ መዘርዝሩን (ሜኑ) ለሁለቱም ሰጠቻቸው፡፡ ሁልጊዜም እንዲህ ናት፡፡ ሰዎች በፍቅር እንዲደላቸው ታስተናግዳለች፡፡ እሷ ግን የፍቅር አካል ሆና አታውቅም፡፡  
አሁንም የሬስቶራንቱ በር ተከፈተና ተዘጋ። ሌሎች ጥንዶች ናቸው፡፡ ሁለተኛው የምሽቱ እንግዶች፡፡  
“ጤና ይስጥልኝ፤ እንኳን ደህና መጣችሁ” አለች በተለመደው የይመስል ፈገግታዋ ታጅባ፡፡
“እናመሰግናለን፤ ለሁለት ሰው ቦታ ይኖርሻል?” አለ ሰውየው፤በእንግዶች ያልተያዙትን በርካታ ጠረጴዛዎች እየቃኘ፡፡
“ቀድማችሁ ቦታ ይዛችኋል ጌታዬ?” ስትል ጠየቀች፤ ጥርሷን ነክሳ ፈገግ እያለች፡፡
“አዎ ይዘናል፤ ዴቪድ ሳንድ  በሚል ስም” አለ - የደንበኞች ስም ዝርዝር የያዘውን መዝገብ ቃኘት እያደረገ፡፡ ሉሲ ዝርዝሩን አይታ የሰውየው ስም ላይ ምልክት ካደረገች በኋላ፤ የተለመደውን ጥያቄ አቀረበች፡፡
“ካፖርታችሁን ልቀበላችሁ?”
ካፖርታቸውን ተቀብላ ፊት ፊት እየመራች ወደተያዘላቸው መቀመጫ ወሰደቻቸው፡፡ ከዚያም  የምግብ መዘርዝሩን (ሜኑ) አቀበለቻቸው፡፡ ቀኑን ሙሉ ተመሳሳይ ስራ! ሁልቀን አታካች ድግግሞሽ፡፡
እንደገና የሬስቶራንቱ በር ተከፍቶ ተዘጋ፡፡
“ጤና ይስጥልኝ” አለች ሉሲ- በፈገግታ!
መቆም-- ከዚያ መነሳት፡፡ እንደገና መቆም--- እንደገና መነሳት፡፡ በራሷ ፍጥነት እንድትጓዝ ወይም መስመሯን እንድትቀይር ጨርሶ አይፈቅድላትም፡፡ ባቡሩ ትዝ አላት፡፡
“እባክሽ ለሁለት ሰው ቦታ” አለች ሴቲቷ፡፡ ሉሲ ጉሮሮዋን ያነቃት መሰለች፡፡
የስም ዝርዝሩን መዝገብ ስትገልጥ ጣቶቿ ይንቀጠቀጡ ነበር፡፡
“ለሁለት ሰው ቦታ--” የሚሉትን ቃላትን አትወዳቸውም፤ ሁሌም ያሳምሟታል፡፡
“ቦታ ይዛችኋል?” ጠየቀቻቸው፤ እንደምንም ፈገግ ለማለት እየሞከረች፡፡
ሴቲቱ ቀድመው መያዛቸውን ነገረቻት። መዝገቡ ላይ ስማቸው መኖሩን አረጋገጠች፡፡ ካፖርታቸውን ተቀብላ መቀመጫቸውን ካሳየቻቸው በኋላ ሜኑውን  አቀበለቻቸው፡፡
እንግዳ መቀበያው ዴስክ ላይ ቆማ በሃሳብ ተውጣለች - ሉሲ፡፡ ከሚያፈቅሩት ጋ የቫለንታይን ቀን ምሽትን ማሳለፍ ምን  ስሜት ይፈጥር ይሆን? ከፍቅረኛ ጋር እንዲህ እራት መብላትስ? ማውራት--መሳቅና መላፋትስ? ---- ሉሲ እኒህን ሁሉ ስሜቶች አታውቃቸውም፡፡
ዴስኩ ላይ እንደቆመች ሬስቶራንቱ ቃኘት አደረገች፡፡ ከአንድ ጠረጴዛ በቀር ሁሉም በጥንዶች ተይዟል፡፡ ከ16 እስከ 60 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ፍቅረኞች ቤቱን ሞልተውታል፡፡ ብዙ ዓይነት ጥንዶች ያሉትን ያህል ብዙ ዓይነት ፍቅርም ይታያል -  አዲስ ፍቅር፣ ያረጀ ፍቅር፣ የከረመ ፍቅር፣ የስርቆሽ ፍቅር፣ የጥድፊያ ፍቅር፣ የይምሰል ፍቅር ወዘተ-- አንዳንዶቹ ጥንዶች በዝምታ ተውጠዋል፡፡ ሌሎች ሳይነካኩ መቀመጥ የሚችሉ አይመስሉም። አንዳንዶች ኮስተር ያለ ጨዋታ ይዘዋል፡፡ ከጣራ በላይ የሚያስካኩም አሉ፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ይላቀሳሉ፡፡ ጠብ ያማራቸውም አልጠፉም፡፡
  ይሄ ሁሉ ፍቅር በሞላበት ክፍል ውስጥ ሉሲ ግን ተደብታለች፡፡ በእዚሁ ሁሉ ሰው መሃል ሆና ብቻዋን ናት፡፡ በዚያ ላይ ሥራው አድክሟታል። እግሯና ወገቧ ደቋል፡፡ ዓይኗ ሊከደን ምንም አልቀረውም፡፡ ከዚህ በኋላ “ለሁለት ሰው ቦታ ይኖርሻል?” የሚል ጥያቄ ባትሰማ ደስታዋ ነው፡፡ ጥንዶች ማየት አንገሽግሿታል፡፡ በሩ ሲከፈት ሰምታ ቀና አለች፡፡ አብሯት ያመሸው የስራ ባልደረባዋ ዘሎ ወጣና፤
“ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ፤ እንኳን ደህና መጡ” በማለት ተቀበለ፡፡
“ጤና ይስጥልኝ፤ ለአንድ ሰው ቦታ ይኖራችኋል?”
ይሄን ነበር ሉሲ ምሽቱን ሙሉ ለመስማት የናፈቀችው፡፡ ከድቅድቅ ብቸኝነት መንጥቆ የሚያወጣትን ይሄን እንግዳ ድምፅ፡፡ አሁን ከአንገቷ ቀና አለች፡፡ ዓይኖቿ በደስታ እንባ ተሞሉ፡፡ በ30ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ ያለ ሰው እንደሆነ ገምታለች፡፡
 እንግዳው በጨረፍታ አየት አደረጋትና ቁራሽ ፈገግታ ወረወረላት፡፡ የእጆቹን መዳፎች እርስ በእርስ እያፋጨ ሬስቶራንቱን ቃኘ፡፡ የሉሲ ልብ በደስታ ጮቤ ረገጠ፡፡ ወጣት ነው፡፡ ጣቱ ላይ ቀለበት አላሰረም፡፡ በቫለንታይን ምሽት ፍቅረኛ ሳይዝ  መምጣቱ ያሳፈረው አይመስልም፡፡
“ለአንድ ሰው ቦታ ይኖራችኋል?” በማለት ያቀረበውን ጥያቄ ደግማ ብትሰማው ተመኘች፡፡
“አዝናለሁ ጌታዬ፤ ቀድመው ካላስያዙ ልናስተናግድዎት አንችልም” የስራ ባልደረባዋ ምላሽ ነበር፡፡
“ምን?” ሉሲ ከቆመችበት ዴስክ ዘላ ወጥታ ባልደረባዋ ላይ አፈጠጠችበት፡፡
በልቧ ውስጥ ስትደንስበት የነበረው የሙዚቃ ሲዲ ተጫጭሮ የቆመ  መሰላት፡፡
“ሉሲ--” አላት ባልደረባዋ - ከእንግዳው ዞር ለማለት እየሞከረ፡፡  
“ምን እያልሽ ነው?” ጠየቃት ግራ በተጋባ ስሜት፡፡
“አንድ ያልተያዘ ጠረጴዛ አለ እኮ” አለችው መስኮቱ አጠገብ ወዳለው ቦታ እያመለከተችው፡፡
 “እሱ እኮ የሁለት ሰው መቀመጫ ነው፤ እንዴት አንድ ሰው ይቀመጥበታል?” አለ በቁጣ
“እስቲ የማይቀመጥበትን ምክንያት ንገረኝ? እንግዳ አይደለም እንዴ!” ሉሲ ሽንጧን ገትራ መከራከር ያዘች፡፡  
“የበለጠ ገንዘብ የምናገኘው እኮ ጥንዶች ሲቀመጡበት ነው” ባልደረባዋ በቁጣ እንደማይሆን ገብቶታል፡፡
“ገንዘብ? ገንዘብ ነው ያልከው?” ተሳለቀችበት፡፡
  ባልደረባዋ አፍሮ ዝም አለ፡፡ ወዲያው የሬስቶራንቱ በር ተከፈተና የረፈደባቸው ጥንዶች እየተሳሳቁ ገቡ፡፡ የሉሲ ባልደረባ ሁለመናው ጥንዶቹ ላይ አነጣጠረ፡፡ ሆኖም ሉሲ ቀደመችው፡፡
“ጤና ይስጥልን---እንኳን ደህና መጣችሁ” አለች ቀልጠፍ ብላ፡፡
“እባክሽ ለሁለት ሰው ቦታ ፈልጊልን?”
ሲያሰለቻት ያመሸውንና ትክት ያላትን  ነገር ነው የሰማችው፡፡
“አዝናለሁ---ለጥቂት ተያዘ” አለቻቸው በትህትና፡፡ ዞር ብላ ባልደረባዋን ተመለከተች። ድፍረት አጣ እንጂ የሆነ ነገር መናገር እንደፈለገ ያስታውቃል፡፡ ጥንዶቹ  ሬስቶራንቱን ለመጨረሻ ጊዜ ከቃኙ በኋላ ተያይዘው ወጡ - እየተሳሳቁ፡፡ ሉሲ በድል አድራጊነት ስሜት ተሞልታ ብቸኛውን እንግዳ እያየች
 “ካፖርትህን ልቀበልህ?” አለችው፤ ልብ የሚያሞቅ ፈገግታ እየፈነጠቀች፡፡
ከካፖርቱ በፊት ብርድ ያቀዘቀዘውን እጁን እያቀበላት “አመሰግንሻለሁ!” አላት፡፡
ልቧ በደስታ ሞቀ፡፡ ካፖርቱን ተቀብላ በሬስቶራንቱ ውስጥ ወደ ቀረው ብቸኛ ጠረጴዛ እየመራች ወስዳ በክብር አስቀመጠችው፡፡
 ወጣቱ እንግዳ ብቻውን ገብቶ ሁለት ሆኖ ወጣ።
ሉሲም  በቫለንታይን ቀን ከብቸኝነት ጋር ተፋታች፡፡  

Published in ልብ-ወለድ
Monday, 10 February 2014 07:47

‘ድፍረት’ ፊልም ተሸለመ

በኢትዮጰያዊው ፊልም ባለሙያ ዘረሰናይ ብርሃኔ ተጽፎ የተዘጋጀው ድፍረት ፊልም፣ በ2014 ሰንዳንስ አለማቀፍ የፊልም ፌስቲቫል በ‘ወርልድ ሲኒማ ድራማቲክ ኦዲየንስ’ ዘርፍ ተሸላሚ ሆነ፡፡
ታዲያስ መጽሄት ከኒዮርክ እንደዘገበው፣ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራውና የ99 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው የዚህ ፊልም ዳይሬክተር ዘረሰናይ ብርሃኔና ፕሮዲዩሰሯ ምህረት ማንደፍሮ ባለፈው ቅዳሜ በተከናወነው የፌስቲቫሉ የመዝጊያ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ሽልማቱን ተቀብለዋል፡፡
በሰንዳንስ አለማቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ በመካፈል የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፊልም የሆነውና በተለያዩ የአሜሪካ ሲኒማ ቤቶች ተዘዋውሮ ሲታይ የሰነበተው ድፍረት፣ በተመልካቾች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት በማግኘቱ ነው በዘርፉ ተሸላሚ ለመሆን የበቃው፡፡
ከፊልሙ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰሮች አንዷ የሆነችው ታዋቂዋ የሆሊውድ የፊልም ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ፣ ከሳምንታት በፊት ድፍረት በኢትዮጵያ የፊልምና የኪነጥበብ ዘርፍ ላይ የራሱን አሻራ ያሳረፈ ስራ ነው ስትል አድናቆቷን መግለጧ ይታወሳል፡፡

        በአፍሪካ ፖለቲካዊና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ በርካታ መፅሃፍትን በመፃፍ የሚታወቁት የፖለቲካ ተመራማሪው ዶ/ር ዴቪድ ሆይሌ “አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ የአውሮፓ ጓንታናሞ ቤይ?” የተሰኘ መፅሃፍ ለንባብ አበቁ።
ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ አፍሪካን ዳግም በቅኝ ግዛት ለመያዝ ታልሞ የተቋቋመ አውሮፓዊ ፍ/ቤት ነው የሚሉት ዶ/ር ዴቪድ፤ አውሮፓ ከ120 ዓመታት በኋላም በተቋሙ አማካይነት አፍሪካውያንን ለመዝረፍ እየሞከረች ነው ብለዋል።
“አውሮፓውያን፤አፍሪካንና ሌሎች ታዳጊ ሃገራትን በዘመናዊ ባርነት ለመግዛት እንዲሁም  ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሉዓላዊነታቸውን ለማሳጣት የሚጠቀሙበት መሳሪያ ነው” በማለት መፅሃፉ ዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍ/ቤት ያብጠለጥላል።
ባለፈው ሳምንት  በመዲናችን በተካሄደው 22ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ የተመረቀውን የዶ/ር ዴቪድ መፅሃፍ ያሳተመው የአፍሪካ የጥናትና ምርምር ማዕከል እንደሆነ ታውቋል። የመጽሐፉ ዋጋ  14.99 ዶላር  ነው፡፡ ዶ/ር ዴቪድ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ አምስት መፅሃፍትን ያሳተሙ ሲሆን በቅርቡም የአሁኑ መፅሃፍ ተከታይ ለንባብ እንደሚበቃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ የኢራን ኢምባሲ የባህል ክፍል የሚዘጋጀው አመታዊው የኢራን የፊልም ፌስቲቫል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በብሄራዊ ትያትር ተካሄደ፡፡
የኢራንን እስላማዊ አብዮት 35ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተከናወነው ይህ የፊልም ፌስቲቫል፣ የሁለቱን አገራት ባህላዊ ግንኙነት የማጠናከርና የኢራን የፊልም ኢንዱስትሪ የደረሰበትን ደረጃ የማስተዋወቅ አላማ እንዳለው በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር አሊ ባህሪኒ በፌስቲቫሉ መክፈቻ ላይ ተናግረዋል፡፡ የኢራን ኢምባሲ የባህል ክፍል፣ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመውን የባህል፣ የትምህርትና የሳይንስ ትብብር መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን ፊልም ለማሳደግ የሚያግዙ ስራዎችን እንደሚያከናውንም ገልጸዋል፡፡
ለሶስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚህ የፊልም ፌስቲቫል ላይ፣ ‘ኤም ፎር ማዘር’፣ ‘ዘ ሶንግስ ኦፍ ስፓሮውስ’ እና ‘ኦን ፉት’ የተሰኙ፣ በአለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ ስኬታማ የኢራን ፊልሞች ለእይታ በቅተዋል፡፡

          በኢትዮጵያ እግር ኳስ የሰሞኑ አበይት መነጋገርያ አጀንዳ የ62 ዓመቱ ሰውነት ቢሻው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት መነሳታቸው ነበር፡፡ ሰውነት ከሃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ ለሱፕር ስፖርት አስተያየት ሲሰጡ ለስንብታቸው በፌደሬሽን ላይ ያቀረቡት ቅሬታ የለም፡፡ በስንብታቸው ማግስት ከዋልያዎቹ በኋላ ዋንኛው ትኩረታቸው ከቤተሰባቸው ጋር ማሳለፍ እንደሆነ የተናገሩት ሰውነት ቢሻው አሰልጣኝነት የማይተውት ሙያቸው እንደሆነ በመግለፅ በአገር ውስጥ የሚወዳደሩ ክለቦችን ወይንም በአፍሪካ ደረጃ ብሄራዊ ቡድኖችን ለማሰልጠን ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
‹‹የአሰልጣኝነት ስራ አስቸጋሪ እና ምስጋና የሚያሳጣ ነው፡፡ የምትወደደው በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ ስትሆን ብቻ ነው፡፡ በህይወት ውስጥ በተለያዩ  ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውጣውረዶችን በፀጋ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ መባረሬ ድንገተኛ ዜና አልሆነብኝም። በደቡብ አፍሪካ ከተደረገው የቻን ውድድር ስንመለስ ከመቅፅበት ሁኔታዎች ሲቀየሩ አስተውያለሁ፡፡ ከስንብቱ በፊት ተዘጋጅቶ በነበረው የግምገማ መድረክ፤ በብሄራዊ ቡድኑ የነበሩ ችግሮችን አስረድቼ ነበር፡፡ ይሁንና ቡድኑ በቻን ተሳትፎው ለገጠመው ውጤት ማጣት እኔ ምክንያት እንደሆንኩ አስቀድሞ የተወሰነ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በነበረኝ ሃላፊነት ባስመዘገብኳቸው ውጤቶች እኮራለሁ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ላገኛቸው ስኬቶች 100 ፐርሰንት ብቃቴን በመስጠት አገልግያለሁ፡፡ ›› በማለት አሰልጣኝ ሰውነት ለሱፕር ስፖርት የስንብት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከተሰናበቱ በኋላ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው  የት ይሄዳሉ የሚል ጥያቄ መነሳት ጀምሯል፡፡ አሰልጣኙ በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የደርሶ መልስ ትንቅንቅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በናይጄርያ ከተሸነፈ በኋላ በማግስቱ ወደ ጊኒ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ሊሄዱ ነው ተብሎ ተወርቶ ነበር። በዚሁ ጊዜም አሰልጣኙ አገሬን ትቼ የትም አልሄድም፤ በብዙ ሺ ዶላሮች እንድሰራላቸው የጠየቁኝ ነበር ግን አልተቀበልኳቸውም፤ ፍላጎቴ በኢትዮጵያ መቀጠል ነው ብለው አስተባብለው ነበር፡፡ ከሳምንቱ አጋማሽ ስንብታቸው በኋላ ደግሞ ከቦትስዋና እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር ለአዲስ ስራ ግንኙነት ፈጥረዋል እየተባለ ነው፡፡
የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ እለት በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ከተደረገው የግምገማና የምክክር መድረክ ከሁለት ቀናት በኋላ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ  ከቀኑ 9 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ልዩ ስብሰባ አድርጓል። ስብሰባው በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና በረዳት አሰልጣኞቻቸው  ቀጣይ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ከዚሁ የስራአስፈፃሚ ስብሰባ በኋላ በማግስቱ ረቡዕ ካሳንቺስ በሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፅህፈት ቤት ስራ አስፈፃሚው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ጠርቷል። ከቀኑ 10 ሰዓት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በጣም በተጣበበ ጊዜ ቢጠራም በርካታ የስፖርት ጋዜጠኞች መገኘታቸውን ያደነቁት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ፤ መግለጫው በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች  ስንብት ላይ ያተኮረ መሆኑን በይፋ ገልፀዋል። ከኤሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የግምገማ እና የምክክር መድረክ፤ ከማክሰኞው የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ እስከ ረቡዕ ጋዜጣዊ መግለጫ የነበሩትን ሁኔታዎች ከዚህ በታች እንደቀረበው ተዳስሰዋል፡፡
ሰውነትና ዋልያዎቹ በባለድርሻ አካላት ሲገመገሙ
ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በተዘጋጀው የግምገማ እና የምክክር መድረክ ላይ ከ59 በላይ የስፖርት ጋዜጠኞች መገኘታቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ በእለቱ  በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና በብሄራዊ ቡድናቸው ላይ የሚደረገው ግምገማ የመጨረሻ ውጤት የሚዲያውን ትኩረት የሳበው ጉዳይ ነበር፡፡ በሙሉ ቀን በተካሄደው የግምገማ እና የምክክር መድረክ ላይ የስፖርት ኮሚሽን ተወካዮች፤ የሙያ ማህበራት ተወካዮች፤ የክለብ አመራሮች፤ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባላትና  ባለሙያዎችና በስፖርቱ ላይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በመክፈቻ ንግግር ባስጀመሩት በዚህ ስብሰባ ላይ በጠዋት ፕሮግራም የፌደሬሽኑ ዋና ፀሃፊ የአስተዳደር ዘርፍ ካቀረቡት ሪፖርት በኋላ በቴክኒኪ ኮሚቴ ሰብሳቢው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን የነበረውን ተሳትፎ በቁጥሮች የመዘነ ግምገማ ተሰጥቷል፡፡ በመቀጠል የቀረበው ደግሞ የቻን ተሳትፎ እንዴት እንደነበር የሚያብራራ የሰውነት ቢሻው መግለጫ ነበር፡፡ በእለቱ የነበሩ ጋዜጠኞች እነዚህ መግለጫዎች ሲቀርቡ ተከታትለዋል፡፡ የአስተዳደር ዘርፉ ሪፖርት የ2 ዓመት ተኩል ስራን በአጭሩ የተነተነ ነበር፡፡ ሪፖርቱ በሰውነት ቢሻው ዘመን የነበረው  ብሄራዊ ቡድን አጠቃላይ የአስተዳደር እና የፋይናንስ ሂደት በአጭሩ መግለፁን የታዘቡ አንዳንድ ጋዜጠኞች የአሰልጣኙ መሰናበት ፍንጭ ነው ብለው ነበር፡፡ በአንፃሩ የሚዲያ ባለሙያዎች በቴክኒክ ኮሚቴው ግምገማ ብሄራዊ ቡድኑን በመዘኑ በቁጥሮች መወሳሰብ ግራ ተጋብተዋል፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴው አሰልጣኙን ከውድድር በኋላ ከመተቸት ከውድድሩ በፊት በቂ መረጃ  በመስጠት ለምን አልሰራም በሚል ቁጭት ብዙዎች ግምገማውን አልተማረኩበትም፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አስገራሚ ማብራርያን ሁሉም ባለድርሻ አካል በትኩረት አዳምጦታል፡፡ ሰውነት በግምገማው መድረክ ያቀቡትን መግለጫቸውን ሲጨርሱ ከብሄራዊ ቡድን ጋር በመስራት ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት በመግለፅ ነበር፡፡ ለጋዜጠኞች ከአሰልጣኙ ማብራርያ ቀልባቸውን የወሰደው በብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ማጣት ተጠያቂ ነኝ ብለው በልበሙሉነት መናገራቸው ነበር፡፡  ይሁንና ዓላማቸው የነበሩትን ልጆች በመያዝ እና አዳዲስ ተተኪዎችን በመፈለግ ብሄራዊ ቡድኑን ለቀጣዩ የሞሮኮው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ እንደሆነ ሲናገሩ ግን ማጉረምረም ነበር፡፡  ፌደሬሽኑ የግምገማ እና የምክክር  መድረኩን ያዘጋጀው በቅርቡ ይፋ ለሚያደርገው የ5 ዓመት መሪ ስትራቴጂክ እቅድ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ለማግኘት አስቦ መሆኑን በመግለፅ ሚዲያዎች በቡድን ለሚደረገው ምክክር እንዲሳተፉ ጋብዞ ነበር። ጋዜጠኞች በመድረኩ መሳተፋቸው ተገቢ አለመሆኑን አምነውበት ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡
በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ዋና ፀሃፊ አቶ ይግዛው በቀረበው የአስተዳደር ዘርፍ ሪፖርት መንግስት በስፖርቱ እየተጫወተ ያለውን ወሳኝ ሚና ጎልቶ ወጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እና ዋና ውድድር፤ በዓለም ዋንጫ 3 ዙር የማጣርያ ምእራፎች፤ በሴካፋ እና በቻን ውድድሮች በነበረው ጉዞ ፌደሬሽኑ በአስተዳደራዊ ዘርፉ ካከናወናቸው ተግባራት የትጥቅ ድጋፎች እና ማበረታቻ ሽልማቶች ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ ዋና ፀሃፊው አቶ ይግዛው ለአሰልጣኞች፤ ለተጨዋቾች፤ ለቡድን መሪዎች፤ ለልዑካኖች እና ልዩ ልዩ አስተዋፅኦ ላደረጉ ሰዎች በድምሩ 14 ሚሊዮን 875ሺ ብር ወጭ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ዋና ፀሃፊው አልገለፁትም እንጂ ብሄራዊ ቡድኑ በነበረው ስኬት በስፖንሰርሺፕ፤ በገቢ ማሰባሰብ እና በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተገኘው ብር ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ነበር፡፡ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ብሄራዊ ቡድኑን በስፖርት ትጥቆች አቅርቦት አለመቸገሩን  የገለፁት ዋና ፀሃፊው ፤ ለብሄራዊ ቡድኑ ከፌደራል ስፖርት ከ1060 በላይ የተለያዩ ትጥቆችን፤ ከኦሎምፒክ ኮሚቴ 236 ቱታዎች መገኘቱን በመጥቀስ መንግስት በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በኩል   ለብሄራዊ ቡድኑ የማበረታቻ እና የምስጋና  ድጋፎችን በመስጠት የነበረው ትኩረት የሚመሰገን ነውም ብለዋል፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ ስኬት የገቢ ምንጮቹን ያሰፋው ፌደሬሽኑ 1116 የስፖርት ቱታዎች ከ886ሺ በላይ በማውጣት ገዝቷል ፤ ብሄራዊ ቡድኑ በልምምድ ስፍራ እንዳይቸገር፤ በመኝታ እና በምግብ  ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ሲያገኝ እንደነበርም  ዋና ፀሃፊው አቶ ይግዛው ገልፀዋል፡፡ በአስተዳደራዊ ዘርፍ የተፈጠረው ችግር የቡድን መሪዎች በየጊዜው እና በዘፈቀድ ሲቀያየሩ ከመቆየታቸው በተያያዘ እንደነበር ዋና ፀሃፊው አቶ ይግዛው በሪፖርታቸው አንስተዋል፡፡  ይሄው ዝርክርክ የፌደሬሽን አሰራር ታሪካዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ብሄራዊ ቡድኑ  በቢጫ ካርድ ቅጣት መሰለፍ ያልነበረበት ተጨዋች አጫውቶ በሰራው ጥፋት ለ3 ነጥብ መቀነስና ለገንዘብ ቅጣት መብቃቱ በአስተዳደር ዘርፉ የታየ የአሰራር ችግር  ነበር ብለዋል፡፡
“በቻን ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የቀረበው የሰውነት ቡድን ፋውል የሚያበዛ፤ የግብ እድሉን የማይጠቀም፤ የአካል ብቃት ችግር የታየበት፤ በስነልቦና ያልጠነከረ፤ በደንብ ያልተዘጋጀ ነበር”  በማለት አሰልጣኙን በመተቸት የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ በግምገማው መድረክ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን የነበረውን ተሳትፎ በቁጥሮች ላይ በተመሰረተ ሪፖርት ፈትሸዋል ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በቻን ተሳትፎው በመብቃቱና በአህጉራዊ መድረክ ያለበትን ደረጃ በማሳየቱ ተጠቃሽ ውጤት መሆኑን የገለፁት ባለሙያው ለወጣቶች መነቃቃት የነበረው አስተዋፅኦ ትልቅ ጥንካሬ እንደሆነና የዜጎች መነጋጋርያ አጀንዳ መሆኑ ይደነቃል ብለዋል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ ድክመቶች በሁለት ነጥቦች እንደሚጠቃለሉ የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሲያስረዱ፤ የመጀመርያው በቻን ተሳትፎ ዋና አሰልጣኙ እና ረዳቶቻቸው ለወጣት እና ተተኪ ተጨዋቾች እድል አለመስጠታቸው በብሄራዊ ቀጣይ እድገት ተፅእኖ የሚፈጥር መሆኑን ባለመረዳት ነው ብለው፤  በሌላ በኩል የብሄራዊ ቡድኑ የተፎካካሪነት ብቃት በውጤት የታጀበ አለመሆኑ በግልፅ ከብዙ ችግሮች ጋር ታይቷል ብለዋል፡፡
የቴክኒክ ኮሚቴው ግምገማ  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን ተሳትፎው ከሊቢያ፤ ከኮንጎ እና ከጋና ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ከ3ቱ ቡድኖች በድምር የሚበልጥ ፋውል እንደሰራ፤ የግብ እድሎችን መጠቀም እንዳልቻለ፤ በኳስ ቅብብል ረገድ ውጤታማ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን እንዳበዛ፤ በአጨዋወቱ ኳስ ወደ ኋላ በመመለስ መጥፎ አዝማሚያ እንዳሳየ፤ በመከላከል ላይ የጥንቃቄ ጉድለት እና ድክመት እንዳለበት፤ ኳስን በጭንቅላት መግጨት እና የተቃራኒ ቡድን ኳሶችን ከአደጋ ነፃ እንደማያወጣ፤ በመስመር ብዙም እንደማይጫወት አመልክቷል። የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ በአጠቃላይ አሰልጣኞች ለብሄራዊ ቡድን በመረጧቸው ተጨዋቾች መሄድ የሚገባቸውን እድል ነፍገው የማይገባቸውን ማሰለፋቸው ዋና ስህተት እንደነበር ሲገልፁ፤ የተጨዋቾች የአካል ብቃት  አለመሟላትና ለስነልቦና ችግሮች መጋለጥ የቡድኑን አቅም ያቃወሱ ምክንያቶችእንደነበሩም ተረድተናል ብለዋል፡፡ አሰልጣኞች ቡድኑን በብቃት እንዳላዘጋጁ፤ ለዝግጅታቸውም ከክለቦች ጋር በቅንጅት ስለማይሰራ በቡድኑ ብቃት ላይ ተፅእኖ መፍጠራቸውንም የቴክኒክ ኮሚቴው ግምገማ አብራርቷል፡፡
ለሰውነት ምስጋና ይግባቸው
የፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ረዳቶቻቸው ቡድኑን ተረክበው ባገለገሉበት ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል እግር ኳሱን ያነቃቁ በርካታ ውጤቶች እና ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ መብቃቱ  የመጀመርያው ድንቅ ስኬት እና አበይት የታሪክ ምእራፍ ነበር፡፡ ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ እስከመጨረሻው የማጣርያ ምዕራፍ በመጓዝ ብሄራዊ ቡድኑ ከአፍሪካ 10 ምርጥ ቡድኖች ተርታ መግባቱም ይታወሳል፡፡  በአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ ቻን ውድድር ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ መሳተፏም ተጠቃሽ ስኬት ነበር፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ባለፈው ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ባስመዘገበው ውጤት በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ያለቅድመ ማጣርያ በቀጥታ ለምድብ ማጣርያ የመወዳደር እድልም አግኝቷል፡፡  
አቶ ጁነዲን ባሻ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል የተገኘውን ስኬት ባጠቃለለ ንግግራቸው ‹‹ ለብዙ ዘመናት ብሄራዊ ቡድኑ ብዙ ጎል የሚገባበት፤ ተከታታይ ሽንፈቶችን የሚያስተናግድ፤ እናሸንፋለን ብለን በአዕምሯችን እንዳናስብ ያደረገን ነበር፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና መላው ቡድናቸው ይህን የቀየረ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ የእግር ኳስ ስሜት አነቃቃትዋል፤ ወደ ስታድዬም  እንዲመጣ አድርገዋል፤ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ተብሎ መታሰብ እንዲጀምር አስችለዋል፡፡  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማልያ ከዳር እስከዳር እንዲለበስም ምክንያት ሆነዋል፡፡›› በማለት  ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በኢትዮጵያ እግር ኳስ በፈጠሩት መነቃቃት እንደ ብሄራዊ ጀግና የሚታዩ ታላቅ ሰው መሆናቸውን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛውጤት አላቸው። በ50ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዛቸው ከፍተኛው ተከፋይ ነበሩ።
በሰውነት የስራ ዘመን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቁ ስኬት ከመመዝገቡም በላይ የአገሪቱ የእግር ኳስ ደረጃ ተሻሽሏል፤ ከዋልያዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ወደ 6 የተለያዩ አገራት ወደ የሚገኙ ክለቦች በመሰማራት በዝውውር ገበያው ተፈላጊነታቸው ጨምሯል፡፡
የሰውነት መሰናበቻ ምክንያቶች
ስራ አስፈፃሚው በዋና አሰልጣኙ ሰውነት ቢሻው እና በረዳቶቻቸው ለተገኙ ውጤቶች ክብርና ምስጋና እንደሚገባ ቢገልፅም በብሄራዊ ቡድኑ ቀጣይ ጉዞ ላይ ባደረገው ልዩ ስብሰባ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል እንቅፋት የነበሩ ድክመቶችን መርምሯል፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራው ብሄራዊ ቡድን ከናይጄርያ ጋር ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የባከኑ እድሎች ነበሩ፡፡ ከዚያም ኬንያ ባዘጋጀችው የሴካፋ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን ለዋንጫ ተጠብቆ ከምድቡ በጊዜ የተሰናበተበት ሁኔታም ብዙ ጥያቄዎችን ፈጥሯል። በመጨረሻም  በደቡብ አፍሪካው የቻን ውድድር ቡድኑ በነበረው ተሳትፎ ደካማ አቋም ማሳየቱ እና የፉክክር ደረጃው ኋላቀር መሆኑ መረጋገጡ ሁሉንም ያሳሰበ ነበር።  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሄራዊ ቡድን ዳግም ወደሽንፈት መመለሱን የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ሲታዘብ ቆም ብሎ ማሰብ እንዳስፈለገው የተናገሩት አቶ ጁነዲን ባሻ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በቀጣይ ወዴት ያመራል፤ መንግስት እና ህዝብ ከስፖርቱ ምን ለውጥ ይፈልጋሉ የሚለውን መክረንበት ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ረዳቶቻቸው በብሄራዊ ቡድኑ ያላቸው ቆይታ ማብቃት እንዳለበት ከውሳኔ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ከስራ እንደተሰናበቱ የተገለፀላቸው   በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ሃላፊዎች፤ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የግምገማ መድረክ ላይ በሃላፊነታቸው ስለመቀጠል ፍላጎታቸው ከተናገሩ 3 ቀናት በኋላ ነበር፡፡ አሰልጣኞቹ መሰናበታቸውን ካወቁ በኋላ ውይይት ተደርጎ በተሰራው ሁሉም መደሰቱን፤ ግንኙነታቸው እንደሚቀጥል፤ ከስፖርቱ ጎን በመሆን እንደሚቀጥሉ ቃል መግባታቸው ተነግሯል፡፡
‹‹ሰዎች ጥሩ ይሰራሉ፡፡ ጊዜዎች ይቀያየራሉ፡፡ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ረዳቶቻቸው በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ደርሶ መልስ ፍልሚያ ከናይጄርያ ጋር፤ በሴካፋ እና በቻን ውድድሮች ይዘው በቀረቡት  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የማሸነፍ ስሜት ቀነሰ፤ የውጤት ማጣት ተከታታለ፤ በእርግጥ ተጨዋቾችም አሰልጣኞችም በጨዋታዎቹ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ በክለቦች መካከል ያለው ውድድር አለማደጉ፤ በታዳጊዎች ላይ የሚሰሩ ተግባራት ያልጠነከሩ መሆናቸው፤ እና የአደረጃጀት እና የአሰለጣጠን ብቃት አለማደግ ለብሄራዊ ቡድኑ ድክመት የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የውጤት ማጣቱ አዝማሚያ የመጣው ባለንበት ልክ እና ደረጃ ነው። እግር ኳስ ያለበትን ደረጃ ቆም ብለን ማሰብ ነበረብን ›› በማለት ለታሪካዊው ውሳኔ ያደረሱ ዝርዝር ሁኔታዎችን አቶ ጁነዲን ባሻ ገልፀዋል፡፡
 በፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በኩል ብሄራዊ ቡድኑ በመቀጠል በ2015 በሞሮኮ ለሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ይፈለጋል፡፡  በታዳጊ እና ወጣት  ቡድኖች አህጉራዊ ውድድሮች ንቁ ተሳታፊ የመሆን ፍላጎትም አለ። የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ለለውጥ ተነሳስተው በዘላቂ ልማትና የእድገት ሂደት  እንዲሰሩ የማስተባበር እቅድም አለ፡፡ በአጠቃላይ የአሰልጣኝ ሰውነት ስንብት ስራውን ከጀመረ 4 ወራት የሆነው የፌዴሬሽን አመራር አዲስ የለውጥ ምእራፍ መክፈቱን ያበሰረበት ነበር፡፡
የአሰልጣኞቹ የኮንትራት ውል መቋረጡ ትልቅ ውሳኔ በመሆኑ በግልፅ መታወቅ አለበት ያሉት ጁነዲን ባሻ፤ አሰልጣኞች ስራቸውን ራሳቸው አልለቀቁም ወይም በክፉ ስሜት አልተሰናበቱም ብለዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙና ረዳቶቻቸው በማንኛውም የሰራተኛ ህግ መሰረት ስንብታቸው እንደሚከናወን የገለፁት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት በክብር እና በምስጋና ይሸኛሉ እንጂ የካሳ ክፍያ የላቸውም ብለዋል፡፡ የስራ አስፈፃሚው አሰልጣኞቹን ለመቀየር መወሰኑን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ሲገልፅ ሌላው የፌደሬሽን ዝርክርክ አሰራርም ተጋልጧል፡፡ የአሰልጣኞቹ የቅጥር ኮንትራት ጉዳይ ነው፡፡ የአንዱ በጥቅምት፤ የሌላው በህዳር የሌላው በታህሳስ ውል የሚያበቃበት ነበር ያሉት አቶ ጁነዲን ባሻ፤ የቅጥር ኮንትራት በግልፅ የሚታወቅ መሆን ቢኖርበትም አሰልጣኞቹ ኮንትራታችሁ አልቋል ብለንና ኮንትራታቸውን አቋርጠን ለማሰናበት ያልፈለግነው፤ የቡድኑን የስራ ስሜት ላለማመሳቀል እና ላለመረበሽ በመወሰናችን ነበር ብለዋል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ፌደሬሽን ሃላፊነቱን ከተረከበ ከ3 ቀናት በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የደርሶ መልስ ማጣርያውን ከናይጄርያ ጋር በአዲስ አበባ ይጀምር ነበር። በሴካፋና በቻን ውድድሮች ከዚያ በኋላ  በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መደረጋቸውን በማገናዘብ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን  በተለይ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የቅጥር ኮንትራት ውል ጥቅምት 28 አብቅቶ በይፋ ኮንትራራታቸው እንደተራዘመ ሳይገለፅ እስከ ታህሳስ 28 እየሰሩ እንዲቀጥሉ መደረጉ ፌደሬሽኑን ያስተቸዋል፡፡  
አሰልጣኞቹ እንዲሰናበቱ የተደረገው በሴካፋ እና በቻን ውድድሮች ላይ ባሳዩት ድክመት ብቻ እንዳልሆነ በመግለጫው የተናገሩት ሌላው የፌደሬሽኑ  የስራ አስፈፃሚ አባል እና ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት  አቶ ተክለወይኒ ናቸው፡፡ በቻን ውድድር የኢትዮጵያ ቡድን ለዋንጫው ትልቅ ግምት ተሰጥቶት እንደነበር ከናይጄርያ እና ጋና ተርታ ይጠቀስ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተክለወይኒ፤ ይህን በመንተራስ የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ከአሰልጣኞቹ፤ ከረዳቶቻቸው እና ከተጨዋቾች ጋር ሲመካከር በቻን ያለው ግብ ዋንጫ ማምጣት ወይም ግማሽ ፍፃሜ መድረስ እንደሆነ ገልፆላቸዋል፡፡  የቡድኑ አባላት ይህን ግብ ለማሳካት ስንት ሽልማት ይጠብቀናል ብለው ሲደራደሩ ደህና ሽልማት ታገኛላችሁ ብለን ተማምነን ነበር ብለዋል፡፡  ከቻን ጉዞ በፊት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ዋና አሰልጣኙ ዋንጫ ለማምጣት ወይም ግማሽ ፍፃሜ ለመድረስ ቃል የገቡትን ካልሆነ ተሸንፎ መመለስ የሚለውን ጨመሩበት፡፡ ተገቢ አልነበረም፡፡ ‹‹በቻን ውጤት ላይ ያደረግነው  የውስጥ ግምገማ ብሄራዊ ቡድኑ ለተሰጠው ግምት በቂ ጥረት አላደረገም ነው፡፡ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ አካላት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ደረጃ በተሳተፈባቸው ውድድሮች ጥሩ መጫወቱን ገልፀውልናል፡፡ ጎንለጎን ግን የቡድኑ ደረጃ ደካማ እንደሆነና የተፎካካሪነት ብቃቱም መሻሻል እንደሚያስፈልገው መክረውናል፡፡ ስለሆነም የአሰልጣኞቹ መቀየር አስፈልጓል›› በማለት አቶ ተክለወይኒ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በየጨዋታው ብዙ የግብ እድሎች አምልጦታል፤ ተጨዋቾቹ ጥሩ ቢጫወቱም ውጤት ግን አላገኙም፤ ለውድድሮቹ በአሰልጣኞቹ የተደረገው ዝግጅት በፕሮፌሽናል መንገድ አልነበረም። ይህ ሁሉ ዝርዝር ምክንያት የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ ትልቅ ክፍተት ብለውታል። ‹‹ያሉብን ክፍተቶች የማይስተካከሉ ከሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው ውጤት መቼም ሊሳካ አይችልም ስለዚህም ስርነቀል ለውጥ ያስፈልጋል በሚል ከመግባባት ላይ ደርሰናል ››ሲሉም ተጨማሪ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወቅታዊ ብቃት ላይ የፊፋ ባለሙያዎች ያደረጉትን ትንተና ለአሰልጣኞቹ መቀየር ተጨማሪ ምክንያት እንደነበር በመግለፅም  ለእግር ኳሱ ጠቅላላ ህዳሴ የሚያመጣ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ ለታመነበት አቅጣጫ ውሳኔው አስፈላጊ ነበር ብለው ተናግረዋል፡፡
የሰውነት  ተተኪ ከየት? ከአገር ውስጥ ከባህር ማዶ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፋፃሚ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ቀላል ስራ አለመሆኑን ትልቅ ሃላፊነት እንደሆነ መገንዘቡን ሰሞኑን ገልጿል፡፡ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና የረዳቶቻቸውን ስንብት የወሰነው ግን በአጣብቂኝ ውስጥ ሆኖ ይመስላል፡፡ ስራ አስፈፃሚው በፕሬዝዳንቱ በኩል አሰልጣኞቹን ያሰናበትነው ሌላ አሰልጣኝ ለመቅጠር በመጓጓት ማለቱም ተስፋ ሰጪ አይመስልም፡፡ በአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት የሚመች አደረጃጀት ለመፍጠር መታሰቡን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ ፤ ቦታውን ክፍት ማድረግ የመጀመርያው ተግባር እንደሆነ መታወቅ እንዳለበት በማስረዳት የህዝብ ጉዳይ ስለሆነ በግልፅ፤ ያለወከባ እና በጥንቃቄ ተገቢው መስፈርት ወጥቶ በሚደረግ ውድድር መሰረት የሚፈፀም እንደሚሆን ቃል ገብተዋል፡፡
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በአዲሱ አሰልጣኝ ቅጥር የመጀመርያ ሙከራ በአገር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን ማሰስ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከሰውነት ቢሻው ስንብት በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ ጋር ስማቸው እየተያያዘ ካሉ የአገር ውስጥ አሰልጣኞች መካከል ስዩም ከበደ፤ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እና ገብረመድህን ሃይሌ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ለአሰልጣኙ ቅጥር ወደውጭ የምንወጣበት ሁኔታ ካለ የገንዘብ ምንጮቻችን በመፈተሽ የምናደርገው ይሆናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡ የቀድሞው የጊዮርጊስ ክለብ አሰልጣኝ የነበረው፤ በሱዳኑ አልሂላል ክለብ የሰራውና በምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ካለው ልምድ ባሻገር የሩዋንዳ እና የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድንን ያሰለጠነው ሰርቢያዊ ሰርዶጆቪች ሚሉቲን ሚቾ ከውጭ አሰልጣኞችቀድሞ ስሙ ተጠርቷል፡፡
በቀድሞው ፌደሬሽን የተገባላቸውቃል ሳይፈፀምላቸው ቅር ተሰኝተው የነበሩት ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌንትም እየተጠቀሱ ናቸው፡፡ ቶም ሴንትፌይት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ሃላፊነት ለመረከብ በይፋ ጥሪ በማክበር የመጀመርያ የውጭ አሰልጣኝ ናቸው።  ከቤልጅዬም ለሱፕር ስፖርት በሰጡት ማብራርያ ‹‹ሰውነት ቢሻው ለብሄራዊ ቡድን ባስገኘው ስኬት ምስጋና ይገባዋል። ረዳቴ ሆኖ አብረን ስንሰራ በነበረበት ወቅት እንደ አስራት መገርሳ እና ጌታነህ ከበደን የመሳሳሉ ተጨዋቾች ለቡድኑ በመምረጥ አስተዋፅኦ ነበረኝ። በእርግጥ አገሪቱን ለቅቄ የወጣሁት ከፌደሬሽኑ ጋር በተፈጠሩ አለመግባባቶች ነበር፡፡ ተመልሼ ብሄራዊ ቡድኑን የማሰልጠን እድል ባገኝ ብዙ ልሰጠው የምችለው ነገር አለ፡፡ በተለይ ዋልያዎቹ በትልልቅ ግጥሚያዎች የሚገጥማቸውን ፈተና የሚወጡበትን አቅም ማስተካከል እችላለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን በፈጠራ እና በቴክኒክ የዳበረ ጥሩ አሰልጣኝ ካገኘ ምርጥ መሆን የሚችል ነው።›› በማለት ቶም ሴንትፌይት ለሱፕር ስፖርት ተናግረዋል፡፡
ፌደሬሽኑ የአሰልጣኙ ቅጥር በቀና መንገድ፤ አሳማኝ መመዘኛ እና መስፈርት ተዘጋጅቶ የሚከናወን እንደሆነ ሲያስታውቅ፤ ፍለጋውን በጋዜጦች ማስታወቂያዎችን በማውጣት፤ የተለያዩ ጥቆማዎችን ከባለድርሻ አካላት እና ከሙያተኞች በመቀበል፤ በብሮድካስት ሚዲያዎች በማስተዋወቅ ይሰራበታል ብሏል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ እንደገለፁት በአሰልጣኝ አዲስ ቅጥር የማፈላለግ ተግባር ላይ  የቴክኒክ ኮሚቴ ሃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ኮሚቴው በአንድ ሳምንት ጊዜ  ለሃላፊነቱ ብቁ የሆኑ ሰዎችን ዝርዝር እንዲያቀርብ ይጠበቃል፡፡
ቀጣዩን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመቅጠር ፌደሬሽኑ ያሰበው የህዝብ ፍላጎት አድጓል፤  ዓለም አቀፍ ደረጃ ይዘን ተፎካካሪ ሆነን እንቅረብ ከሚል አቅጣጫ በመነሳት ነው፡፡ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው መሰናበት  በኋላ ግን ለብሄራዊ ቡድኑ የሚመጥን አሰልጣኝ ፍለጋው ፈታኝ እንደሚሆን  መገመቱ  ስጋትን የጋረጠ ሆኗል፡፡
በአገር ውስጥ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ተተኪ ለማግኘት አሁን ጊዜው የሚያስቸግር ይመስላል፡፡ ብቁ ናቸው የሚባሉ አሰልጣኞች በአመዛኙ  በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ብዙም ልምድ የሌላቸው፤ የሙያ ብቃታቸው ያን ያህል የማያስመካ፤ አንዳንዶቹ በክለብ አሰልጣኝነት ሃላፊነታቸውን ለመልቀቅ የሚቸገሩ ናቸው፡፡ እነዚህ እና ሌሎችም ምክንያቶች ተተኪ አሰልጣኝ ከአገር ውስጥ የማግኘቱን እድሉን ያጠብበዋል፡፡ ከአገር ውጭ አሰልጣኝ ለመቅጠር ደግሞ ከዚህ በፊት ያሉ ተመክሮዎች የሁኔታውን አስቸጋሪነት በይበልጥ ያጎሉታል፡፡ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በፊት ሁለት የውጭ አገር አሰልጣኞች ነበሩ፡፡  በትውልድ ናይጄርያዊ ሆነው ስኮትላንዳዊ ዜግነት ያላቸው አሰልጣኝ ኢፌም ኦኑራ እና ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌንት ናቸው፡፡
ሁለቱም አሰልጣኞች ከብሄራዊ ቡድን ጋር የነበራቸው ቆይታ አወዛግቧል፡፡ ከዚያ በፊት የነበሩትን ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ዲያጎ ጋርዚዬቶ እና የፌደሬሽኑ እሰጥ አገባም በማስታወስ  ብዙ ልምድ መቅሰም ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን ብቁ ናቸው ተብለው ከውጭ የመጡ አሰልጣኞች ያለው መጥፎ አመላከት ካልተወገደ የሚያሳስብ ይሆናል፡፡ የውጭ አሰልጣኞች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የማሰልጠን ሃላፊነቱ በምቹ ሁኔታ በነፃነት እንዲሰሩበት  የተሰጣቸው አልነበሩም፡፡ በቂ የስራ ጊዜ በኮንትራት ውላቸው አያገኙም ነበር፡፡  
ከአገር ውስጥ ባሉ አሰልጣኞች ምንም አይነት ክብር አይሰጣቸውም፤ ተባብሮ ከመስራት ይልቅ እንደውም ለውጥ አያመጡም በሚል አስተሳሰብ ዘመቻ ሲደረግባቸው አጋጥሟል፡፡ በሌላ በኩል ለአሰልጣኞቹ የሚከፈለው ደሞዝ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መጠየቁም ይፈትናል፡፡  ብዙውን ጊዜ የውጭ አገር አሰልጣኞች ቅጥር  ለማከናወንና ክፍያ በመፈፀም ፌደሬሽኑ እቅዱን  እውን የሚያደርገው ክቡር ሼህ አላሙዲ ድጋፍ ላይ በመተማመን ነበር። ክቡር ሼህ አላሙዲ ይህን አይነቱን ድጋፍ መስጠት ካቆሙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አስቀድመው የነበሩ ድጋፎችም በተለያዩ መንገዶች ሲመዘበሩ እና ሲባክኑ ማጋጠሙም ጥሩ ታሪክ አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአሰልጣኞቹ የቅጥር ሁኔታ ላይ ፌደሬሽኑ ከየትኛው አካል ጋር ተመካክሮ እንደሚሰራ፤ በምን አይነት መስፈርት አወዳድሮ እንደሚቀጥር እና ለምን እንደቀጠረ በግልፅ ሁኔታ ያልተሰራበት ሆኖ መቆየቱን ማስታወስ ይቻላል። ሌላው ዋና አደጋ የውጭ አገር አሰልጣኞች ከተቀጠሩ በኋላ የሃላፊነት ቆይታቸው በአላስፈላጊ ጫናዎች ሲያጥር፤ በአሰለጣጠን ፍልስፍናቸው እና በቋንቋቸው ከብሄራዊ ቡድን ጋር መግባባት ሲያዳግታቸው፤ ከአገሪቱ ሚዲያዎች ጋር ተቀራርበው ለመስራት ሲቸገሩ እና ከፌደሬሽኑ አካላት ጋር መግባባት ሲሳናቸው እንደነበር ማስታወሱ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ውድደሮች በብቁ ተፎካካሪነት እንዲሳተፍ የሚያበቃውን ፕሮፌሽናል አሰልጣኝ  እንዴት ሊያገኝ ይችላል ብቻ ሳይሆን ከተገኘስ የሚጠይቀውን ውድ ክፍያ ማን ይችላል የሚሉ ጥያቄዎች ስጋት ይፈጥራሉ። የሊቢያን ብሄራዊ ቡድን በማሰልጠን በቻን ውድድር ዋንጫ ለማንሳት የቻሉት ፈረንሳዊው ሃቪዬር ክሌሜንቴ ደሞዛቸው እስከ 20 ሺ ዶላር ነው፡፡ በአጠቃላይ አንድ የውጭ አገር አሰልጣኝ ለመቅጠር በወቅቱ የገበያ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከ15 እስከ 20 ሺ ዶላር በወር መክፈል ሊኖርባት ይችላል፡፡ ይህ ገንዘብ ታድያ ከየት ይመጣል፤ ከሼህ አላሙዲ ወይንስ ከመንግስት መልስ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው፡፡
ከሰውነት በኋላ ፌደሬሽኑ እና የህዳሴ ስትራቴጂው
በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው የግምገማ እና የምክክር መድረክ ላይ ከፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት በመቀጠል የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አንበሴ እንየው ነበሩ። ኮሚሽኑ እንደመንግስት የእግር ኳሱ ከፍተኛ ባለድርሻ አካል መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ አንበሴ፤  እግር ኳስ አንጋፋ እና ፈርቀዳጅ ስፖርት እንደሆነ በመግለፅ የህዝብ አጀንዳና አንድ የልማት ጉዳይ ስለሆነ የግምገማ እና የምክክር መድረኩ በስፖርቱ ህዝብን የሚያስደስት እና የሚያረካ ውጤት ላይ ለሚደረስበት የለውጥ እንቅስቃሴ መነሻ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በቀድሞው ፌደሬሽን አማካኝነት ከ2004 እሰከ 2007 በሚል የ3 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ በሚል ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በተወሰነ መልኩ እቅዱን ማሳካት መቻሉን አመልክተዋል፡፡ ወደፊትም በተሻለ ሁኔታ መሰራት ስላለበት  በአሁኑ ፌደሬሽንም በስትራቴጂክ እቅድ መመራት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ አቶ አንበሴ እንየው እግር ኳስ የእድገታችን ልዩ መገለጫ መሆን አለበት የሚል ማሳሰቢያቸው  መንግስት ለስፖርቱ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ያረጋገጠ ነበር፡፡ በየክልሉ በርካታ ስታድዬሞች እየተገነቡ ናቸው፡፡ አካዳሚዎችም ተመስርተዋል፤ እየተሰሩም ናቸው፡፡  መንግስት በስፖርቱ ሊገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እና የአገር መልካም ገፅታ ገብቶታል፡፡ የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት በመንግስት በኩል ለስፖርቱ  የተሰጠውን ትኩረት ያህል ብዙ መስራት እንዳለባቸው መረዳት ይገባል፡፡
በእግር ኳስ ኢትዮጵያ አሸንፋ እንድትወጣ ሁሉም ይፈልጋል ያሉት አቶ ጁነዲን ባሻ፤ በስፖርቱ ኢንቨስትመንት እስከዛሬ ከተደረገው የበለጠ ማሳደግ አለብን ይላሉ፡፡ እንደ ጋና አይነት አገራት በርካታ ታዳጊ ፕሮፌሽናሎችን በማፍራት በአሁኑ ጊዜ ከ354 በላይ ተጨዋቾች በላይ በመላው ዓለም በማሰማራት ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውን ማጥናት እንደሚያስፈልግ ያስረዱት ፕሬዝዳንቱ ፤ ኢትዮጵያ ወጣት ፕሮፌሽናሎችን ለማውጣት ምን መስራት እንዳለባት፤ ስንት አካዳሚዎች ይበቁናል ስንት አካዳሚዎች አሉን እንዴት እንስራባቸው በሚል መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የስራ አስፈፃሚው እንደሚያስበው በኢትዮጵያ እግር ኳስ የወደፊት ጉዞ ላይ አሰልጣኝ መቀየር ብቻ ለውጥ አያመጣም፡፡ በእርግጥ የዋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ቁልፍ ሃላፊነት ቢሆንም ጎን ለጎን በስፋት ለውጥ የሚያስፈልጋቸውም ሁኔታዎችም አሉ፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን የማስፈፀም ብቃት እና አደረጃጀት ለውጥ እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል፡፡ በወጣቶች አና ታዳጊዎች ላይ ባተኮረ ስትራቴጂ ከስርመሰረቱ ካልተሰራ አሰልጣኝ ተጨዋች ሊያገኝ አይችልም በሚል አስተሳሰብም ለውጥ ለመፍጠር ታስቧል፡፡ የስራ አስፈፃሚው አባላት እንደገለፁት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ለሚያስችለው ስትራቴጂክ እቅድ የባለሙያ ቡድን ተቋቁሞ ሰነዱ እየተዘጋጀ ነው፡፡  በየካቲት ወር ሰነዱ ሙሉ ተዘጋጅቶ የሚያልቀው ይህ የስትራቴጂ እቅድ በአምስት አመት መርሃ ግብር የተነደፈ መሆኑ ተገልፆ አሁን ያለው ፌደሬሽን በስልጣን ላይ በሚቆይባቸው ቀሪዎቹ 3 ዓመታት በስፋት እንደሚሰራበት፤ ለሚቀጥለው የፌደሬሽን አመራር የሚያወርሰው እንደሚሆንም ተስፋ ተደርጓል፡፡ የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ እንደገለፁት በዚሁ የስትራቴጂ ሰነድ ላይ ከ300 እስከ 400 የሚደርሱ ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብ ውይይት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለ ጠቁመው በስትራቴጂክ እቅዱ መሰረት የብሄራዊ ቡድኑ አጠቃላይ አደረጃጀት እና መዋቅር፤ አሰራሩ፤ የሰው ሃይል አደረጃጀቱ በአጠቃላይ እንደሚገመገም እና በተገቢው  መንገድ ከተሰራበት ለውጥ መፍጠር እንደሚቻል ፅኑ እምነት አለን ብለዋል፡፡ በስትራቴጂክ እቅዱ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፕሮፌሽናላይዝድ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ስራ አስፈፃሚው ተስማምቶበታል፡፡
በዚህ የፕሮፌሽናሊዝም አቅጣጫ መሰረት የፕሪሚዬር ሊግ፤ የብሄራዊ ሊግ እና ሌሎች የወጣት እና ታዳጊ ውድድሮች ፕሮፌሽናላይዝድ ማድረግ እነደሚያስፈልግ፤ የክለቦችን አቅም እና አደረጃጀት በማሳደግ ፕሮፌሽናላይዝድ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል እንደሚገባ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት እንደከፍተኛ የሰው ሃይል በመጠቀም እግር ኳሱ እንደኢኮኖሚው አድጎ እንዲታይ መሰራት አለበት በሚል ነው፡፡ በወጣት እና በታዳጊ ፕሮጀክቶች፤ መንግስት፤ ክለቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በስፋት እንዲንቀሳቀሱም ይደረጋል፡፡
የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ ሃጎስ እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል የሚችለው በእውቀት እና በስትራቴጂ እቅድ ሲሰራበት፤ የፕሮፌሽናሊዝም አቅጣጫዎችን ሲከተል ነው ፡፡ በዚህ ረገድ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የፌደሬሽን ስራ አመራር ብዙ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅበትና ኢትዮጵያ ዛሬ በከፍተኛ ደረጃ የሚያፎካክረውን ስፖርት የሚመጥን ደረጃ አግኝታ እንደ ብራዚል ፤ እንደ ስፔን እና እንግሊዝ ተጠቃሚነት እንዲኖራት በመመኘት መስራት ያስፈልጋል በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የፍ/ቤቱን ሸፍጥ ያጋለጡት አውሮፓዊ በአፍሪካ መሪዎች ተደንቀዋል
አፍሪካን ቅኝ ለመግዛት የሚደረግ አዲስ ኩሸት ነው ተብሏል
“አውሮፓ የሚሏት እርም የለሽ አህጉር፣ እነሆ ከአንድ መቶ ሃያ አመታት በኋላም አፍሪካንና አፍሪካውያንን ለመዝረፍ እየሞከረች ነው!” አሉ እንግሊዛዊው የፖለቲካ ተመራማሪ ዶክተር ዴቪድ ሆይሌ፡፡
“አውሮፓውያን ያቋቋሙትን ‘አለማቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት’ የተባለ መላ ተጠቅመው አፍሪካውያንን ባህር አሻግረው እያጋዙ፣ ሆነ ብለው በሰየሙት የይስሙላ ችሎት ላይ እያቆሙ ነው” ሲሉ ደገሙ ዶክተር ዴቪድ ሆይሌ፡፡
ይህም በአዳራሹ ውስጥ የነበሩ በርካቶችን በደስታ አፍለቀለቀ፡፡ ዙሪያ ገባውንም በጭብጨባ አደበላለቀ፡፡ እርግጥም የሰውዬው ንግግር ብዙዎችን ማስደሰቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ አዳራሽ ውስጥ ከታደሙት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች አብዛኞቹ፣ ከአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ጋር ቂም የተያያዙና በባላንጣነት የሚተያዩ ናቸው፡፡
በአፍሪካ ፖለቲካዊና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ በርካታ መጽሃፍትን ለንባብ በማብቃት የሚታወቁት የፖለቲካ ተመራማሪው ዶክተር ዴቪድ ሆይሌ፣ ባሳለፍነው ሳምንት በዚሁ በአዲስ አበባ በተካሄደው 22ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ነበር፣ የአገራቱ መሪዎች በተገኙበት ሁለት መጽሃፍቶቻቸውን በይፋ ያስተዋወቁት፡፡
በአፍሪካውያን መሪዎች ተጨብጭቦላቸው ከተመረቁት የዶ/ር ዴቪድ ሆይሌ መጽሃፍት አንዱ፣ ‘የአለማቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ የአውሮፓ ጓንታናሞ ቤይ?’ የሚል ርዕስ አለው፡፡ መሪዎቹ ያጨበጨቡት ለርዕሱ ብቻ አይደለም፡፡
“አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፣ ለአውሮፓውያን አፍሪካን እንዳትረጋጋ በማድረግ፣ ፖለቲካዊ የበላይነቷን የማሳጣትና የማዕድን ሃብቷን በገፍ የመዝረፍ ድብቅ አጀንዳቸው ማስፈጸሚያ ሆኖ ከርሟል!... ተቀማጭነቱ በሄግ የሆነው ፍርድ ቤቱ፣ አፍሪካን እንደገና ቅኝ ለመግዛት የሚደረግ አዲስ አውሮፓዊ ኩሸት መገለጫ ነው!...” ለሚለው መደምደሚያው ጭምር እንጂ፡፡
ዶክተር ዴቪድ እንደሚሉት፣ ፍርድ ቤቱ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 130 በላይ አገራት ተፈጸሙ በተባሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችና ወንጀሎች ዙሪያ ከ8ሺህ 300 በላይ የክስ ማመልከቻዎች ቢደርሱትም፣ እስካለፈው የፈረንጆች አመት 2013 መጨረሻ ድረስ የወንጀል ምርመራ የጀመረው በ8 አገራት ላይ ብቻ ነው፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ ሰውዬው እንደገለጹት፣ የፍርድ ቤቱን ተልዕኮ ጥያቄ ውስጥ የሚከተው ሌላው አስገራሚ ነገር፣ እነዚሁ ስምንት አገራትም ሁሉም አፍሪካዊ መሆናቸው ነው - ኡጋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የመካከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኮትዲቯር፣ ማሊና ሊቢያ፡፡
“አንድ እንኳን አፍሪካዊ ያልሆነ አገር፣ በፍርድ ቤቱ የወንጀል ምርመራ እየተደረገበት አይደለም። ራሱን አለማቀፍ የፍትህ ተቋም አድርጎ የሰየመው ይህ የይስሙላ ፍርድ ቤት፣ በአፍጋኒስታንና በኢራቅ የሰሯቸውን የጦርነት ወንጀሎች በተመለከተ በቂ ማስረጃ ከያዘባቸው የተለያዩ አውሮፓ አገራት መንግስታት፣ አንዱን እንኳን ለፍርድ ለማቅረብ አልደፈረም!... ይህም የተቋሙን አድሏዊነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል” ብለዋል ዶ/ር ዴቪድ፡፡
የአውሮፓን ‘ሸፍጥ’ ባጋለጠው አውሮፓዊ የባዳ ዘመዳቸው፣ ዶ/ር ዴቪድ ልባቸው ቅቤ የጠጣ የአፍሪካ መሪዎችም፣ “እኛም ሰሚ አጥተን ነው እንጂ፣ ለፍትህ ቆሜያለሁ እያለ ፍትህን ስለሚገድለው ስለዚህ ወገኛ ተቋም ቀድመን ተናግረናል” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል፡፡
አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ እ.ኤ.አ በ2013 በኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታና በምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ ላይ ክስ መመስረቱን ተከትሎ፣ የፍርድ ቤቱ ጉዳይ ከአፍሪካ ህብረት ቀዳሚ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች አንዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ህብረቱ በዚህ ተቋም ላይ እምነት እንደሌለውና አካሄዱም አህጉሪቱን ክፉኛ የሚጎዳ ህገወጥ ተግባር እንደሆነ በይፋ ከመናገር አልፎ፣ በአህጉሪቱ መንግስታት ላይ የሚሰነዝረውን ውንጀላም መሰረተ ቢስ ሲል አጣጥሎታል፡፡
ህብረቱ በጥቅምት 2013 በጠራው የመሪዎች ልዩ ጉባኤ ላይ የአለማቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እውቅና የሚነሳ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ተሰሚነት ያላቸው የአህጉሪቱ ቁልፍ መሪዎችም፣ በተቋሙ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በተለያዩ አህጉራዊና አለማቀፋዊ መድረኮች ላይ ማስተጋባታቸውን ቀጥለዋል፡፡
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ “አፍሪካ ላይ ወዳነጣጠረ የፖለቲካ መሳሪያነት ዘቅጧል” ሲሉ በይፋ የተቹትን ይሄን ፍርድ ቤት፤ የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዮሪ ሙሴቬኒም እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ዘልፈውታል፡፡
የመፅሃፉ ደራሲ ዶ/ር ዴቪድም የአፍሪካ መሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በተቋሙ ላይ የሚሰነዝሯቸውን ትችቶች የሚደግፍ ንግግር ነው በህብረቱ ጉባኤ ላይ ያሰሙት፡፡ “ራሱን አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እያለ የሚጠራው የውሸት ፍርድ ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያከናወናቸውን ተግባራት ተመልከቱ፡፡ እጅግ ብዙ የመሰሪነት ስራዎችና ተንኮሎችን ሲጎነጉን፣ የአፍሪካ አገራትን በማስፈራራት አልያም መደለያ በማቅረብ በግዳጅ የፍርድ ቤቱ አባል ሆነው እንዲቀጥሉ ሲሞክር እኮ ነው የኖረው!” በማለት፡፡
በህብረቱና በአለማቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት መካከል የተፈጠረው የጠላትነት ስሜት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደጉን ተከትሎ፣ የአፍሪካዊ መንግስታት አለማቀፍ ወንጀሎችን የሚዳኝ የራሳቸውን ክልላዊ የፍትህ ተቋም ወደመፍጠር እንዲገቡ አስገድዷል፡፡
ዶ/ር ዴቪድ እንደሚሉት፤ አውሮፓውያን ይሄንን የአፍሪካ ህብረት አማራጭ ለማሰናከል በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር መድበው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1998 በአለም ዙሪያ የሚገኙ 122 አገራትን በአባልነት ይዞ በተመሰረተው አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፣ 34 አገራትን የፍርድ ቤቱ አባላት በማድረግ ከሁሉም አህጉራት ቀዳሚ የሆነችው አፍሪካ ናት፡፡ “ፍርድ ቤቱ 18 የእስያ ፓሲፊክ፣ 18 የምስራቅ አውሮፓ፣ 27 የካረቢያንና 25 የምዕራብ አውሮፓ አገራትን በአባልነት ቢይዝም፤ ጣቱን የቀሰረው ግን በፈረደባት አፍሪካ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህ ነው ፍርድ ቤቱን ፍትሃዊነት በጎደለው ሁኔታ ፍትህን አስከብራለሁ ብሎ የሚዳክር የይምሰል ተቋም የሚያደርገው” ብለዋል ዶክተር ዴቪድ፡፡
በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ጥናት በማድረግ የሚታወቁት ዶ/ር ዴቪድ፤ ስለ አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጸረ - አፍሪካ ተቋምነት ሲናገሩ ቅንጣት ታህል ማመንታት አይታይባቸውም።
“አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አውሮፓዊ ተቋም ነው፡፡ አፍሪካን እዳኛለሁ ብሎ የተነሳ አውሮፓዊ ፍርድ ቤት ነው፡፡ እውነታው ይሄና ይሄ ብቻ ነው!!” በማለት ነው፣ ዶ/ር ዴቪድ በህብረቱ 22ኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው በሙሉ ልብ የተናገሩት፡፡ ይህ የዶክተሩ ንግግር፣ አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ ለፍርድ ይቅረቡ ብሎ በወሰነባቸውና ከችሎት ፊት ሊገትራቸው በሚፈልጋቸው በእነኡሁሩ ኬንያታና ኦማር ሃሰን አል በሽር ልብ ውስጥ ትልቅ ደስታ ፈጥሯል፡፡
ዶ/ር ዴቪድ ሆይሌ ለንባብ ያበቁት አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ የአውሮፓ ጓንታናሞ ቤይ?’ የተሰኘና 345 ገጾች ያሉት መጽሃፍ፤ አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አጠቃላይ ዓላማና የመጨረሻ ግብ፣ አፍሪካን መልሶ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር ማድረግ እንደሆነ ያትታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ራሱን እንደገለልተኛና ከአድልኦ የጸዳ ተቋም አድርጎ ለማሳየት ቢጥርም እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው ባይ ናቸው ዶክተሩ፡፡
ፍርድ ቤቱ 60 በመቶ የሚሆነውን በጀቱን የሚያገኘው ከአውሮፓ ህብረት እንደመሆኑ፣ በአውሮፓ አገራት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በድፍረት ለማጋለጥና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ሞክሮ እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡ ይልቁንም ፍርድ ቤቱ፣ እጅ ያጠራቸውንና ከአጋሮቹ ጋር የፖለቲካ ንክኪ ያላቸውን የአፍሪካ አገራት እየመረጠ በመወንጀል፣ እድሜ ዘመኑን የገፋ የአውሮፓውያን ተላላኪ ነው ይላሉ፤ ዶክተሩ በመጽሃፋቸው፡፡
“አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለመውጣትና ነጻነቷን ለመጎናጸፍ ለዘመናት ታግላለች፡፡ ትልቅ መስዋዕትነትም ከፍላለች፡፡ አሁን ደግሞ ከወደ አውሮፓ ዘመን የወለደው ሌላ ‘ህጋዊ’ የቅኝ ግዛት ሙከራ እየተሰነዘረባት ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ ዝም ማለት የለባትም፡፡ መክታ መመለስ እንጂ!” ብለዋል ጸሃፊው፡፡
ዶ/ር ዴቪድ በመጪው መጋቢት ወር በይፋ ለንባብ ያበቁታል ተብሎ የሚጠበቀውና ‘ጀስቲስ ዲናይድ፣ ዘ ሪያሊቲ ኦፍ ዘ ኢንተርናሽናል ክሪሚናል ኮርት’ የሚል ርዕስ በሰጡት ሁለተኛው መጽሃፋቸውም፣ ፍርድ ቤቱ በአፍሪካ አህጉር ላይ አነጣጥሮ እየሰራ ያለውንና ለወደፊትም ሊሰራ ያሰባቸውን ኢ-ፍትሃዊ ተግባራት በዝርዝር ይዳስሳል ተብሏል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የአደገኛ እጾች መዘዝ
የልብ በሽታ
የአዕምሮ መዛባት
የእንቅልፍ እጦት
ተስፋ የመቁረጥ ስሜት
ጭንቀትና መደበት
ራስን የማጥፋት ፍላጎት

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሣይኮሎጂ ትምህርት ዘርፍ የአራተኛ ዓመት ተማሪ እያለ ነው ካናቢስ የተባለውን አደንዛዥ እፅ መጠቀም የጀመረው፡፡ ለከፋ ጉዳትና ውስብስብ ችግር እንደሚዳርገው፣ የልጅነት ህልሙን እንደሚያጨናግፍበትም ፈጽሞ አላሰበም፡፡
በትምህርቱ ከሰቃዮቹ ተርታ ሚመደበው ቢኒያም (ስሙ ለዚህ ፅሁፍ የተቀየረ) ፤የቤተሰቦቹና የመምህራኑ ሁሉ ተስፋ ነበር፡፡ ይሄም ሌት ተቀን በትምህርቱ እንዲተጋና የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግብ ጉልበት ሆነው፡፡ የሶስተኛ ዓመት ማጠቃለያ ፈተና ሲቃረብ፣ አንዳንድ የክፍሉ ተማሪዎች “አስጠናን” በሚል ሰበብ እየቀረቡት መጡ፡፡ ጥያቄዎቻቸውን በደስታ እየመለሰ፣ የሚያውቀውን እያስረዳቸውና አብረው እያጠኑ ለጥቂት ጊዜያት  አብሯቸው ዘለቀ፡፡ ይሄኔ ነው ለዛሬ ውድቀቱ መነሻ ወደሆነው ሱስ ይዘውት የገቡት፡፡
ስፍራው ስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ ጀርባ ከሚገኙት መቃሚያ ቤቶች ባንዱ ነው፡፡ ጓደኞቹ የመቃሚያ ቤቱ ፀጥታና ድባብ ለጥናት ምቹ እንደሆነ አሳምነው ነው  ቢኒያምን ወደዚህ  ቤት ያመጡት። እሱ ቀደም ብሎ የማያውቀውና ያለመደው አዲስ ነገር በማየቱ ለጊዜው ስሜቱ ተረባበሸ፡፡ ሆኖም አንድ እንጨት ንከስ እያሉ ከሚሰጡት ጫት ጋር ለመላመድ ብዙም ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ሁኔታው ተመቸው ወይም በእሱ አማርኛ “ሙዱ ገባው”፡፡ የሶስተኛ ዓመት ትምህርቱን አጠናቆ ወደ አራተኛ ዓመት የተዛወረው በቀድሞው ከፍተኛ ውጤት አልነበረም፡፡ ሆኖም ቢኒያምን ብዙም አላስጨነቀውም፡፡ ዩኒቨርስቲው ለእረፍት ሲዘጋ ከእነዚሁ ጓደኞቹ ጋር እዚያችው ቤት እየተቀጣጠረ አብሮ መዋሉን ቀጠለበት፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ጓደኞቹ አልፎ አልፎ ተደብቀው የሚያጨሱትን ነገር ለማየትና ለመቅመስ፣ ስሜታቸውንም ለመጋራት ጉጉት ያደረበት፡፡ ይቅርብህ ያለው ማንም አልነበረም፡፡ ጓደኞቹ እጿን አቃምሰው ሱሰኛ ሊያደርጉት ወይም በእሱ አማርኛ “ሊከትቡት” ቋምጠው ነበርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የመጀመሪያው ቀን ስሜቱ የተረጋጋ አልነበረም፡፡ እንደ ሲጋራ ተጠቅልሎ የሚጨሰውን ነገር ሰጥተውት አንድ ሁለቴ እንደሳበ፣ ሃይለኛ ሳልና የማስመለስ ስሜት ገጠመው፡፡ አይኑ እንባ አዝሎ ራስ ምታት ለቀቀበት። “ሳብ ሳብ አድርግበት ይተውሃል” አሉት ጓደኞቹ፡፡ እንደተባለው አደረገ፡፡ እውነትም ፍርሃቱና ድብርቱ ከላዩ ላይ ተገፈው ሲሄዱ ታወቀው፡፡ ደስ ደስ የሚል ስሜት ተሰማው፡፡ ጥንካሬና ሁሉን እችላለሁ አይነት ስሜት ሁለመናውን ወረረው፡፡
ከዚህ ስሜትና ደስታ ርቆ የቆየባቸውን ዓመታት በከንቱ እንደባከኑ ቆጥሮ ተፀፀተ፡፡ ቀስ በቀስ በሱሱ ተጠመደ፡፡ ትምህርቱን በአግባቡ መከታተል ሁሉ ተሳነው፡፡ ምግብ መብላትና ራሱን መጠበቅ እርግፍ አድርጐ ተወ፡፡  ሰውነቱ ከእለት ወደ እለት እየሳሳና እየመነመነ ሄደ በሽተኛ መምሰል ጀመረ፡፡ ቤተሰቦቹ ሁኔታው እጅግ አስደነገጣቸው፤ ሁኔታውን በድብቅ ለመከታተል ሞክረው ደረሱበት፡፡ በልጃቸው ላይ የደረሰው ችግር እጅግ ያሳሰባቸው ወላጆቹ፤ ልጃቸውን በቁጣም፣ በምክርም በልመናም ከገባበት ለማውጣት ብዙ ጣሩ፡፡ ሆኖም አልተሳካላቸውም። “በእኔ ህይወት ውስጥ ማንም አያገባውም” የሚል ሆነ ምላሹ፡፡ የቀድሞ ውጤቱን የሚያውቁ አንዳንድ መምህራን፤ የቢኒያምን  የውጤት ማሽቆልቆል እያዩ ማለፍ አልቻሉም፡፡ ቀስ እያሉ በምክር ለመመለስ ሞከሩ፡፡ ምክሩ ግን  ቢኒያምን የበለጠ እንዲሸሽ አደረገው፡፡ “ምን እየሆንክ ነው?” የሚለው የመምህራኑ ጥያቄ ከትምህርት ገበታው ላይ አራቀው፡፡ ወደ ዩንቨርስቲው መሄዱን ከእነአካቴው ተወው፡፡
የአራተኛ አመት ትምህርቱን ከሁለት ሴሚስተር በላይ መዝለቅ አልሆነለትም፤ ከዩኒቨርስቲው ተባረረ። መባረሩ ቢኒያምን ባያስደነግጠውም ቤተሰቦቹ ግን በጣም አዘኑ፡፡ ይባስ ብሎ ሰውነቱ መንዘፍዘፍና አንዳንዴም ራሱን መሳት ጀመረ፡፡ በህይወት የመቆየቱ ጉዳይ ያሳሰባቸው ወላጆቹ፤የስነልቡና ባለሙያዎች እንዲያዩትና የጤና ክትትል እንዲያደርጉለት አማኑኤል ሆስፒታል አስገቡት፡፡ ወራትን በፈጀ ተከታታይ ህክምና፣ ቢኒያም ወደ ቀድሞ ጤንነቱ እየተመለሰ ይገኛል። በአደገኛ እፅ ሱሰኝነት ሳቢያ የደረሰበትን ችግር ያጫወተኝም የእፅ ሱሰኛ በነበረበት ወቅት ምግብ በአግባቡ ባለመመገቡ ምክንያት በጨጓራውና በአንጀቱ ላይ የደረሰውን የጤና ችግር ለመታከም ኢትዮ - ጠቢብ ሆስፒታል አግኝቼው ነው፡፡
እንደ ቢኒያም አይነት ታሪክ ያላቸው በርካታ ወጣቶች፣ ከትምህርት ገበታቸውና ከሥራቸው  በአደገኛ እፅ ሱሰኝነት ተፈናቅለው፣ የወደፊት ተስፋቸውና ህልማቸው ተጨናግፎ ማየት ዛሬ ዛሬ የተለመደ ይመስላል፡፡ በየትምህርት ቤቶች በራፍ ላይ፣ እንዲሁም  በየመንደሩና በየጉራንጉሩ ውስጥ ቤታቸውን ለአደገኛ እፆች መጠቀሚያነት ያዋሉ በርካቶች የብዙዎችን ህይወት እያጨለሙ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ወቅቶች እነዚህን በድብቅ አደገኛ እፆችን ያስጨሳሉ የሚባሉትን ቦታዎች በድንገተኛ ፍተሻና አሰሳ ሲዘጋና ባለቤቶቹንም ሲያስቀጣ  መቆየቱ የሚታወቅ ቢሆንም ከአሰሳው የተረፉት ወይም ሊደርስባቸው ያልቻሉት ቤቶች፣ ዛሬም ብዘዎችን ለከፋ ሱሰኝነትና የጤና ጠንቅ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ መልኮች እየተጠቀለሉ የሚጨሱ አደገኛ እፆች በየትምህርት ቤቶች ደጃፍ፣ በየመዝናኛ ስፍራዎች፣ በመቃሚያ ቤቶችና በናይት ክለቦች በግልፅ ይሸጣሉ፡፡ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ እሪ በከንቱና ዶሮ ማነቂያ፣ አውቶቡስ ተራ፣ ጐጃም በረንዳ፣ ጣሊያን ሰፈርና ዳትሰን ሰፈር አደንዛዥ እፆቹ ያለከልካይ በአደባባይ የሚሸጡባቸው ስፍራዎች ናቸው፡፡
የአደንዛዥ እፆችና የህገወጥ መድሃኒቶችን ዝውውርና አጠቃቀም በተመለከተ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች፣ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይጠቁማሉ፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ያወጣው መረጃ  እንደሚያመለክተው፣ ህገወጥ የአደገኛ እፆች ዝውውር በየዓመቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ከአራት መቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ሲሆን ከአንድ መቶ አርባ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችም  እጅግ አደገኛ የሆኑ እፆች ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት በ2012 ዓ.ም ላይ ይፋ ያደረገውና The African Drug Nexus የተሰኘ  ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ አደገኛ እፅ ተጠቃሚዎች ያሉባት ሀገር ነች፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት በዚህ ጥናት ውስጥ ካካተታቸው አስር የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ጠቁሞ፣ ከአገሪቱ ህዝብ 1.6 በመቶ በላይ የሚሆነው የአልኮልና አነቃቂ መድሃኒቶች ተጠቃሚ ናቸው ብሏል፡፡ ከእፅ ተጠቃሚ ዜጎች መካከል ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዙት የጐዳና ተዳዳሪዎች እንደሆኑ የገለፀው ሪፖርቱ፤ 85 በመቶ ያህሉ  የጐዳና ልጆች ቢያንስ የአንድ አይነት አነቃቂ እፅ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
ይኸው የአደገኛ እፆች ዝውውርና አጠቃቀም በተለይ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ እየጨመረ እንደሄደም ይኸው ጥናት አመላክቷል፡፡ በተለይ አምራች ሃይል የሆነውና ተስፋ የሚጣልበት ወጣቱ ትውልድ፤የእነዚህ መድሃኒቶችና እፆች ዋንኛ ተጠቃሚ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይሄ አስጊ ሁኔታ  በአጭሩ  መቀጨት  እንዳለበት የገለፀው ጥናቱ፤ ካልሆነ ግን  ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማስከተሉ አይቀሬ ነው ብሏል፡፡
በአገራችን በህገወጥ መንገድ በስፋት እየተመረተ ለገበያ የሚቀርበው እፀፋሪስ ከሚባለው ተክል የሚገኘውና ካናቢስ የተሰኘው አደንዛዥ እፅ ሲሆን በአገሪቱ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውልና ከሌሎች አደንዛዥ እፆች ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ዋጋ ያለው እፅ ነው፡፡ ተክሉ በአገራችን በተለይም በደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል እየተመረተ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን ካናቢስ እየተባለ የሚጠራው ከደረቀው አፀፋሪስ ቅጠልና አበባ የሚገኘው ክፍል ነው፡፡ እፁ አዕምሮን የማዛባትና የማሳት ባህርይ እንዳለው የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከተክሉ ግንድ የሚገኘውና ሬዚን እየባለ የሚጠራው እፅ ደግሞ አነስተኛ በሆነ ዋጋ ገበያ ላይ የሚገኝና በአገራችን አብዛኛዎቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚጠቀሙት እፅ ነው፡፡ ይህ እፅ የአዕምሮ መዛባት፣የማመዛዘን ችሎታን ማጣትና የሳንባ ካንሰርን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከካናቢስ ሌላ በአለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገራችን ጥቅም ላይ ከሚውሉ የአደንዛዥ እፅ አይነቶች መካከል ሄሮይን፣ አምፊታሚንስ፣ ኮኬይን፣ ሞርፊን፣ ፔቲዲን፣ ማታደንና ከዴይን የሚባሉት ይገኙበታል፡፡ እፆቹ በመርፌ፣ በእንክብል፣ በሲጋራና በሱረት መልክ በጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በአገራችን አነዚህን አደንዛዥ እፆች መጠቀም፣ ማዘዋዋር፣ ማምረትና ለተጠቃሚ ማድረስ በህግ የሚያስጠይቁ ወንጀሎች ናቸው፡፡ ሆኖም ቁጥጥሩ የላላ እንደሆነ አንዳንድ ወገኖች ይናገራሉ፡፡
አለም አቀፍ እፅ አዘዋዋሪዎች ኢትዮጵያን እንደመተላለፍያ ስፍራ የሚጠቀሙባትም ቁጥጥሩና ክትትሉ አነስተኛ በመሆኑ እንደሆነ እነዚሁ ወገኖች ይገልፃሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከኮሎምቢያና ከሜክሲኮ ወደሌሎች አገራት ለማዘዋወር ታስቦ በሰው ሆድ ዕቃ ውስጥ ወደ አገራችን የገባ ሔሮይን የተባለ አደንዛዥ እፅ፣ በእፅ አመላላሹ ሶማሊያዊ  ሆድ ዕቃ ላይ በደረሰ ጉዳት ሳቢያ ችግሩ ታውቆ፣ በቀዶ ጥገና  ከሰወየው ሆድ ውስጥ የወጣለት ቢሆንም የሰውየው ህይወት አልፏል፡፡ በርካታ አገራት በእፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወስዱት እርምጃና ቅጣት እጅግ ከፍተኛ ሲሆን  በአንዳንድ አገራት ቅጣቱ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡
አደንዛዥ እጽ  በግለሰብ፣ በቤተሰብ ብሎም በአገር ላይ ከሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በተጨማሪ በተጠቃሚዎቹ  ላይ የሚያስከትለው የጤና ቀውስም ቀላል አይደለም፡፡ የስነ አዕምሮ ሀኪሙ ዶክተር አሳየኸኝ መንግሥቱ ይህንን  አስመልክተው ሲናገሩ፣ አደገኛ እፆች የምግብ ፍላጐትን ማሳጣት፣ የልብ በሽታን፣ የአዕምሮ መዛባትን፣ የማመዛዘን ችሎታን ማሳጣት፣ የአዕምሮ መናወጥ፣ የመተንፈሻ አካላት ችግሮችን፣ የአተነፋፈስ ስርአትን ማዛባት፣ የእንቅልፍ እጦት፣ ተስፋ የመቁረጥ ስሜትን፣ ጭንቀትና መደበትን፣ እንዲሁም ራስን ለማጥፋት የመፈለግ ስሜትን ያሳድራሉ፡፡ የሰውነት መንዘፍዘፍ፣ ራስን መሳትና ድንገተኛ ሞትም የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች እጣ ፈንታዎች ናቸው ብለዋል፡፡ የእፁ ተጠቃሚዎች አዕምሮአቸውን እንደልብ ማዘዝ ስለማይችሉ  አመፅ፣ አስገድዶ መድፈርና መሰል ከባድ ወንጀሎችን እንዲፈፅሙ ይገፋፋሉ ሲሉም ገልፀዋል፡፡ በአብዛኛው አደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች እፁን በጋራ በሚጠቀሙባቸው መርፌዎች የሚወስዱ በመሆኑ፣ አችአይቪን ጨምሮ በደም ንክኪ ለሚተላለፉ በሽታዎች እንደሚጋለጡም ዶክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች በማንኛውም ጊዜና ወቅት ከሱሳቸው መላቀቅ እንደሚችሉ የተናገሩት ዶክተሩ፤ሱሰኞቹ ረዘም ያለ የስነልቡና ክትትልና ህክምና በማድረግ፣ ወደ ቀድሞው ህይወታቸው መመለስ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉት አደንዛዥ እፆች መካከል ሄሮይን የተባለው ከፍተኛ ስቃይን በማስታገስ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ጊዜያዊ የደስታ ስሜትንም ይፈጥራል፡፡ ኮኬይን የተባለው አደንዛዥ እፅ ደግሞ በአንዳንድ አገራት ከአንገት በላይ ማለትም ለአፍ፣ ለአፍንጫ፣ ለጆሮና ለጉሮሮ ቀዶ ህክምና ማደንዘዣ በመሆን ያገለግላል፡፡    

Published in ዋናው ጤና

ጠበቃቸው ሰኞ ይግባኝ ይጠይቃሉ
የትላንትናው የፍ/ቤት ክርክርና ውሳኔ

በአዲስ ጉዳይ ሳምንታዊ መጽሔት የጥር ወር እትም ላይ “ከኢህአዴግ ፍርድቤቶች ፍትህ አይገኝም” የሚል ሃሳብ የተካተተበት ጽሑፍ በማውጣት፤ ፍርድ ቤት ገለልተኛ እንዳልሆነ በመግለፅ ዘልፈዋል ተብለው የተከሰሱት የአንድነት ፓርቲ የምክር ቤት አባል አቶ አስራት ጣሴ ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው ተከራከሩ፡፡ በኋላ የዋስ መብት ተከልክለው ታሰሩ፡፡  
አቶ አስራት በመጽሔቱ ላይ ባወጡት ጽሑፍ “ከሰሞኑ የአኬልዳማ ድራማ በድጋሚ በተከታታይ እየቀረበና እየታየ ነው፡፡ ይህ እየሆነ ያለው አንድነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅትን በስም ማጥፋት ወንጀል በፍ/ቤት ከስሶ ገና ውጤት ባልተገኘበት ወቅት ነው፡፡ ክሱም ፍትህ ከኢህአዴግ ፍ/ቤቶች ይገኛል ተብሎ ሳይሆን በታሪክ ምስክርነት እንዲመዘገብ ሲባል ነው” በሚል ፍ/ቤቱ ገለልተኛ አይደለም ሲሉ ዘልፈዋል ይላል - የክስ ቻርጁ፡፡
አቶ አስራት በትናንትናው ዕለት በከፍተኛው ፍ/ቤት ዘጠነኛ የፍትሃብሄር የቤተሰብ ችሎት ከጠበቃቸው አቶ ተማም አባቡልጋ ጋር ቀርበው በጠበቃቸው በኩል ተከራክረዋል፡፡ “ለምን ፍርድ ቤቱን ዘለፉ?” በሚል ከዳኛዋ ለቀረበው ጥያቄ፣ አቶ ተማም “ደንበኛዬ ተከሰው የቀረቡት በፍትሃብሔር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 480 መሰረት ሲሆን እዚህ ችሎት ቆመው ያሰሙት ዘለፋ የለም፣ በችሎቱ ላይም አልነበሩም፤ አንቀፅ 480 ከችሎት ውጭ ለተፈፀመ ጉዳይ አያገለግልም” የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡
ችሎትን በመዝለፍ አንቀጽ 480፣ ክስ ሊቀርብባቸው የሚችሉ ሶስት አካላት እንዳሉ የገለፁት ጠበቃው፤ ከሳሽ፣ ተከሳሽ እንዲሁም ችሎቱን የታደሙ ታዛቢዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ክሱ የሚቀርበውም ዳኝነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት የችሎቱን ክብር የሚነካ ዘለፋ ያቀረቡ እንደሆነ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
የአኬልዳማን ጉዳይ በተመለከተ  ከአንድነት ፓርቲ ክስ ቀርቦ በሂደት ላይ ያለው በዚህ ችሎት እንደሆነ የጠቆሙት ዳኛዋ፤  “አቶ አስራትም በመፅሔቱ ላይ ይህን ገልፀው ፅፈው እንዴት ችሎት አልዘለፉም ትላላችሁ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ጠበቃው ሲመልሱም፤ “ደንበኛዬ በአጠቃላይ በኢህአዴግ የፍርድ ቤት አደረጃጀት ላይ ችግር እንዳለ ገለፁ እንጂ ይህን ችሎት በተናጠል የዘለፉበት አንዳችም አመላካች ነገር የለም” ብለዋል፡፡ “የደንበኛዬ መጣጥፍ  የኢህአዴግ የፍርድ ቤት ችግር፣ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና የሚመለከት እንጂ ከፍ/ቤት ዘለፋ ጋር አይገናኝም” ሲሉም ተከራክረዋል፡፡
አንቀፅ 480 ስለችሎት ዘለፋ ካሰፈራቸው ውስጥ “ጉዳዩ በተሰራበት ጊዜ” የሚል እንዳለ ለፍ/ቤቱ የጠቆሙት ጠበቃው፤ ደንበኛቸው በችሎት ላይ እንዳልነበሩ፣ የዚህ ችሎት ተከራካሪ እንዳልሆኑ፤ ተከሰው የቀረቡት መፅሄት ላይ አስተሳሰባቸውንና እውነት ነው ያሉትን ነገር በማንፀባረቃቸው ስለሆነ ጉዳዩ “ከክርክር ስነ-ስርዓት ውጭ” ተብሎ በነፃ እንዲሰናበቱ በአፅንኦት ጠይቀዋል፡፡
“ይህን ችሎት አይደለም የተናገሩት የምትሉት ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ በሌላ ችሎት ክርክር አቅርባችኋል?” በሚል የተጠየቁት ጠበቃው፤ ከዚህ በፊት እንዳልተከራከሩ ጠቅሰው የደንበኛቸው መጣጥፍ የሚያጠነጥነው “ጅሀዳዊ አራካት” ከሚለው ዶክመንታሪ ጋር በተያያዘ ሲባልና ሲነገር ስለነበረው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረት እውነት ነው ያሉትን ሀሳብ መፃፋቸውን የጠቀሱት ጠበቃው፤ መጣጥፉ የሽብርተኝነት ህጉ ለኢትዮጵያ ተገቢ እንዳልሆነ፣ ኢህአዴግ ከሽብር ይልቅ ሰላምን እንደሚፈራ፣ በአጠቃላይ ኢህአዴግ ያቋቋመው ፍርድ ቤት የአደረጃጀት ችግር እንዳለበት የሚገልፅ ይህን ችሎት በተናጠል አልዘለፈም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ “ደንበኛዬ በችሎት ተገኝተው እንዳልዘለፉ በፖሊስ በኩል የላካችሁት የክስ መጥሪያ ምስክር ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረት አንድ ሰው ስለፍርድ ቤትም ሆነ ስለማንኛውም ጉዳይ የመናገር፣ የመፃፍና አስተሳሰቡን የማንፀባረቅ መብት እንዳለው ለችሎቱ ያስረዱት ጠበቃው፤ በአንቀፅ 29(6) መሰረትም አንድ ሰው አስተሳሰቡን ሲያራምድ፣ ሲፅፍና ሲናገር ገና ለገና ይህን ያመጣል በሚል ሊገደብ እንደማይገባና ሀሳቡን በማንፀባረቁ ተጠያቂ ሊሆን እንደማይገባ አቶ ተማም አስረድተዋል፡፡
ክርክሩ ከተካሄደ በኋላ ጉዳዩ ለውሳኔ ከሰዓት በኋላ 8፡30 የተቀጠረ ሲሆን፤ ፍ/ቤቱ ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት የአቶ አስራት ጣሴ ጉዳይ በወንጀል የሚያስጠይቅ ሆኖ ስለተገኘ፣ የዋስትና መብታቸው ተከልክሎ በሚቀጥለው አርብ የካቲት 7 ቀን 2006 ዓ.ም ውሳኔ እስኪያገኙ በጊዜያዊ ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ አቶ አስራትም በተለምዶ “አምስተኛ” እየተባለ ወደሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል፡፡
ጠበቃቸው አቶ ተማም አባቡልጉ ውሳኔውን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ ደንበኛቸው በተከሰሱበት የፍትሃብሄር ስነ-ስርዓት ህግ አንቀፅ 480 ጥፋተኛ ቢባሉ እንኳን የገንዘብ መቀጮ እንጂ ለእስር እንደማያበቃ ገልፀው፤ ውሳኔው ላይ ሰኞ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ “ፍ/ቤቱ በወንጀል ያስጠይቃቸዋል ብሎ ወደ እስር ቤት ልኳቸዋል፤ ነገር ግን እኛ በወንጀል ያስጠይቃቸዋል ብለን አናምንም” ያሉት አቶ ተማም፤ “አቶ አስራት የችሎት ስም አልጠሩም፣ አልዘለፉም፤ ይህ ችሎት መጽሔት ላይ በፃፉት ፅሁፍ ጠርቶ ሊጠይቃቸውም አይችልም ብለዋል፡፡ አንድ ሰው በአንቀፅ 480 የሚከሰሰው ችሎት ውስጥ ተገኝቶ ሲዘልፍ ብቻ እንደሆነና አቶ አስራት ግን በጉዳዩ እንደሌሉበት በጠዋቱ የችሎት ውሎ መከራከራቸውን ጠበቃው አስታውሰው፤ ፍቤቱ የሰጠው ውሳኔ ከክሱ ጋር ግንኙነት ስለሌለው ሰኞ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡   

Page 8 of 13