Saturday, 20 December 2014 13:13

“ቪዳ” ፊልም ዛሬ ይመረቃል

በሶኒያ ኖዬል ተደርሶ በሚኪያስ ጌታሁን የተዘጋጀው “ቪዳ” የተሰኘ ፊልም ዛሬ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በፍቅር ታሪክ ላይ በሚያጠነጥነው በዚህ ፊልም ላይ ሶኒያ ኖዬል፣ ሲያምረኝ ተሾመ፣ ጀምበር አሰፋ፣ አንዷለም ደጀኔ፣ ንፁህ ኃይሌ፣ መስፍን ጋሻውና ሌሎችም አንጋፋና ወጣት ተዋንያን እንደተወኑበት ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሠር አሁንም ከአፍሪካ 2ኛ ሆናለች

  • ጋዜጠኞችን ለስደት በመዳረግና ስደተኛ ጋዜጠኞችን በመቀበልም ተጠቅሳለች
  • ሶሪያ “የጋዜጠኞችን ህይወት የበላች አገር” በሚል ተወግዛለች

  አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ አመት በመላው ዓለም 220 ጋዜጠኞች መታሠራቸውንና ቻይና በቀዳሚነት የጋዜጠኞች ሲኦል መሆኗን ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርቱ ያመለከተ ሲሆን ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሠር በአለም 4ኛ፣ በአፍሪካ ኤርትራን አስቀድማ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በኢትዮጵያ በ2014 እ.ኤ.አ የታሣሪ ጋዜጠኞች ቁጥር ከአምናው ከሰባት እጥፍ በላይ ጨምሮ ወደ 17 ከፍ ማለቱን የድርጅቱ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ በኢትዮጵያ ጦማሪያን ጭምር መታሰራቸውንና ከወትሮው በተለየ በርካታ ጋዜጠኞች መሠደዳቸውንም አመልክቷል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ ጋዜጠኞችን በማሰር ተወዳዳሪ ያልተገኘላት ቻይና፤ 44 ጋዜጠኞችን ዘብጥያ እንዳወረደች በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ አምና በሀገሪቱ ታስረው ከነበሩት 32 ጋዜጠኞች ሌላ ዘንድሮ 12 ተጨማሪ ጋዜጠኞች መታሠራቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ቻይና ለጋዜጠኞች ሲኦል መሆኗን አጠናክራ ቀጥላለች ብሏል፡፡ ሁሉም ጋዜጠኞች የመንግስትን ፖሊሲና አሰራር በመንቀፋቸውና አበክረው በመተቸታቸው ለእስር እንደተዳረጉም ተጠቁሟል፡፡ ኢራን ደግሞ ከቻይና ለጥቃ በሁለተኛነት ተቀምጣለች፡፡ የታሣሪ ጋዜጠኞች ቁጥር ከዓምናው በአምስት ያህል ቢቀንስም አሁንም ከዓለም ለጋዜጠኞች የማትመች ሁለተኛዋ ሀገር ሆናለች ብሏል - ሪፖርቱ፡፡ አምና በኢራን 35 ጋዜጠኞች ታስረው የነበረ ሲሆን ዘንድሮ አምስቱ ተለቀው 30ዎቹ በእስር ላይ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች የታሰሩበት ምክንያት እንደማይታወቅ ተገልጿል፡፡ በአለም ላይ ጋዜጠኞችን በማሠር የሚስተካከላቸው አልተገኘም ተብለው ከተለዩት 10 ሀገራት መካከል ኤርትራና ኢትዮጵያ በ3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን እነሱን በመከተል ቬትናም፣ ሶሪያ፣ ግብፅ፣ በርማ፣ አዘርባጃንና ቱርክ ተጠቅሰዋል፡፡
በኤርትራ ስለታሰሩት 23 ጋዜጠኞች ጥናት ለማድረግ መሞከሩን የጠቆመው ሲፒጄ፤ ለበርካታ አመታት የታሠሩ ጥቂት ጋዜጠኞች በህይወት መኖራቸውን ከማረጋገጡ ውጪ በምን ምክንያት እስከዛሬ እንደታሠሩ ለማወቅ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያና ግብፅ ከቀደመው አመት ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ ጋዜጠኞችን እንዳሰሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ግብፅ የአልጀዚራ ጋዜጠኞችን ጨምሮ 12 ጋዜጠኞች ማሠሯን ጠቅሶ የታሠሩበት ምክንያት ግን አልታወቀም ብሏል፡፡ ጋዜጠኞችን በማሰር በ8ኛ ደረጃ የተቀመጠችው በርማ፤ “መንግስትን ተቃውማችኋል” በሚል 10 ጋዜጠኞችን ያሰረች ሲሆን፤ አብዛኞቹም የ10 አመት ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ በአዘርባጃን 9 ጋዜጠኞች ወህኒ ቤት የሚገኙ ሲሆን ዘንድሮ ብቻ አራት የማህበራዊ ሚዲያ “የመብት ተሟጋቾች” በሀገሪቱ ያለውን ሙስናና የሠብአዊ መብት ጥሰት በመተቸታቸው ከያሉበት ተለቃቅመው ለእስር መዳረጋቸው ተጠቁሟል፡፡ ከሁለት አመት በፊት ጋዜጠኞችን በማሠር በ1ኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ቱርክ፤ ዘንድሮ በርካታ ጋዜጠኞችን ከእስር በመልቀቅ ደረጃዋን አሻሽላ፣ 10ኛ ሆናለች፡፡ በአሁን ሰአት በቱርክ 7 ጋዜጠኞች ታስረው እንደሚገኙም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በአህጉር ደረጃ ለጋዜጠኞች ተስማሚ ሆናለች ተብላ የተጠቀሰችው አሜሪካ ነች፡፡ የኩባና የሜክሲኮ መንግስታት እያንዳንዳቸው አንድ ጋዜጠኛ ከማሠራቸው ውጪ አህጉሪቱ ሠላማዊ ነች ብሏል - ሪፖርቱ፡፡ የCPJ ሪፖርት እንደሚጠቁመው፤ ከ2012 ወዲህ በመላው ዓለም 220 ጋዜጠኞች የታሰሩ ሲሆን፤ 132ቱ መንግስትን ተቃውማችኋል ወይም ሽብርተኛ ናችሁ በሚል ለእስር ሲዳረጉ፣ 45ቱ የታሠሩበት ምክንያት አይታወቅም ተብሏል፡፡ ከታሣሪዎቹ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች እንደሆኑ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ቁጥራቸው 83 እንደሚደርስም ጠቅሷል፡፡ የተቀሩት ተቀጣሪ ያልሆኑ እንዲሁም የሬዲዮ፣ ዌብሣይት፣ ቴሌቪዥንና ማህበራዊ ሚዲያ ጋዜጠኞች እንደሆኑ ገልጿል፡፡የታሳሪ ጋዜጠኞችን ቁጥር በየዓመቱ እያበራከቱ ነው ተብለው ከተጠቀሱት ሃገራት መካከል ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ቻይና፣ ባንግላዲሽ፣ ታይላንድ፣ አዘርባጃን፣ ባህሬን፣ ግብፅ፣ እስራኤልና ሳውዲ አረቢያ እንደየቅደም ተከተላቸው ከ1ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ የያዙ ሲሆን ዘንድሮ አንድም ተጨማሪ ጋዜጠኛ ባለማሰራቸው ከተጠቀሱት መካከል ካሜሩን፣ ስዊዘርላንድ፣ ሜክሲኮ፣ ኩባ፣ በርማና ቤላሩስ ይገኙበታል፡፡ ሲፒጄ እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2014 “በአለማቀፍ ደረጃ የጋዜጠኞች ሁኔታ ምን ይመስላል?” በሚል ባካሄደው ጥናት፤ 404 ጋዜጠኞች በደረሰባቸው ጫና የትውልድ ሃገራቸውን ጥለው ለመሰደድ እንደተገደዱ አረጋግጧል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ጋዜጠኞች በብዛት ከተሰደዱባቸው ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በ4ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ 41 ጋዜጠኞች ሃገር ለቀው ወጥተዋል ተብሏል፡፡ 76 ጋዜጠኞችን ለስደት በመዳረግ ፊትአውራሪ የሆነችው ደግሞ ኢራን ናት፡፡ ሶርያ 44፣ ሶማሊያ 42 ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ በማድረግ በሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኤርትራ 29፣ ኩባ 18፣ ፓኪስታን 15፣ ሲሪላንካ 14፣ ሩዋንዳ 11፣ ጋምቢያ 10 ጋዜጠኞች ከሃገር እንዲሰደዱ በማድረግ ከ5-10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘውታል፡፡
ስደተኛ ጋዜጠኞች የተቀበሉ ሃገራት ተብለው ከተለዩ 10 ሃገራት መካከልም ኢትዮጵያ የምትገኝ ሲሆን ዘጠኝ ስደተኞች በመቀበል ከዓለም በ9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ አሜሪካ፣ ኬንያ፣ ቱርክ፣ ፈረንሳይ፣ ኡጋንዳ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ሱዳን፣ እንግሊዝ ከ1-8ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ ሊባኖስ 10ኛ ሆናለች፡፡
አፍሪካ ብዙ ጋዜጠኞች ከተሰደዱባቸው አህጉራት ቀዳሚዋ ስትሆን 165 ጋዜጠኞች በተጠቀሱት አመታት አገራቸ    ውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ መካከለኛው ምስራቅና የእስያ አገራት ይከተላሉ ተብሏል፡፡
በጥናቱ እንደተጠቆመው፤ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጋዜጠኞች እስራትና ክስ ሽሽት ከሃገራቸው የወጡ ሲሆን የስደት አገር ከገቡ በኋላ 21 በመቶ ያህሉ ብቻ በሚወዱት የጋዜጠኝነት ስራ የመቀጠል እድል አጋጥሟቸዋል፡፡ ከተሰደዱት ጋዜጠኞች ውስጥ ወደ ትውልድ ሃገራቸው መመለስ የሚፈልጉት 5 በመቶ ብቻ እንደሆኑም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያን ያላካተተው “ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን” ሪፖርት
በአለማቀፍ ደረጃ ጋዜጠኞች በሙያቸው የሚጋፈጧቸውን ጫናና ተግዳሮቶች እየመዘገበ በየዓመቱ ሪፖርት የሚያቀርበው “ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን” (Reporters without Borders) ዘንድሮ (በ2014) በአለም ዙሪያ 66 ጋዜጠኞች መገደላቸውንና 119 ታፍነው መወሰዳቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገው ቡድኑ፤ ሶርያን “የጋዜጠኞችን ህይወት የበላች ሃገር” በማለት በቀዳሚነት አውግዟታል፡፡ በጦርነትና በእርስ በርስ ግጭት በምትታመሰው ሶርያ፤ ዘንድሮ ብቻ 15 ጋዜጠኞች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ የእስራኤልና የፍልስጤም ግጭት የሰባት ጋዜጠኞችን ህይወት ሲነጥቅ፣ በዩክሬን ተቀስቅሶ የነበረው ጦርነት የስድስት ጋዜጠኞችን ህይወት ቀጥፏል፡፡
በሊቢያና በኢራቅ በእያንዳንዳቸው አራት ጋዜጠኞች ህይወታቸውን እንዳጡም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በአመቱ የተገደሉት የጋዜጠኞች ቁጥር ከአምናው አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ በ2013 በመላው ዓለም የተገደሉ ጋዜጠኞች ቁጥር 71 እንደነበር አስታውሷል፡፡ከቀደመው አመት ሲነፃፀር የሟቾች ቁጥር አነስተኛ ነው ቢባልም በስራቸው ላይ እያሉ በታጠቁ ቡድኖች ታፍነው ደብዛቸው የጠፋ ጋዜጠኞች ቁጥር ጨምሯል ብሏል ሪፖርቱ፡፡ አምና 87 ጋዜጠኞች የታፈኑ ሲሆን ዘንድሮ 119 ጋዜጠኞች ታፍነው እንደተወሰዱ ተጠቁሟል፡፡ በዩክሬን 33፣ በሊቢያ 29፣ በሶርያ 27 እንዲሁም በኢራቅ  20 ጋዜጠኞች በስራቸው ላይ ሳሉ በታጠቁ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸውም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
ዘንድሮ 178 ጋዜጠኞች ከሙያቸው ጋር በተያያዘ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን በቻይና 29፣ በኤርትራ 28፣ በኢራን 19፣ በግብፅ 16 እንዲሁም በሶርያ 13 ጋዜጠኞች በፍ/ቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ዘንድሮ “የእስላማዊ መንግስት አራማጅ ቡድን”፣ ጋዜጠኞችን በአደባባይ በሰይፍ መቅላቱን ያወገዘው ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን፤ ጋዜጠኞች ላይ የተሰነዘረ አዲስ የጥቃት ስልት ነው ብሎታል፡፡ ምን ያህል ጋዜጠኞች በቡድኑ ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው ግን አልጠቀሰም፡፡ቡድኑ ከአፍሪካ ለጋዜጠኞች የማይመቹ ሃገራት ብሎ የጠቀሳቸው ግብፅ፣ ሊቢያና ኤርትራን ሲሆን ኢትዮጵያ በሪፖርቱ አልተካተተችም፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

በደራሲ እሙሼ የተፃፈውና 11 ታሪኮችን ያካተተው “ከበረዶ ስር ፍሞች” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ መፅሃፉ በስደት ላይ አተኩሮ የተዘጋጀ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፀሐፊው ለዘጠኝ ዓመታት በሰው አገር በስደት የኖረ ሲሆን ስደት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነና የቱን ያህል መብት አልባ እንደሚያደርግ በታሪኮቹ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ “የበረዶ ስር ፍሞች” በ172 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ40 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “የጨለማ ግሳቶች” የተሰኘ መፅሃፍ ማሳተሙ ይታወሳል፡፡

Saturday, 20 December 2014 13:01

ቤተ-ሳይንስ እና ቤተ-ሙከራ

       የእኛ ቤተሰብ ባለ ሁለት ሀይማኖት ነው፡፡ በአባቴ በኩል የቤታችን ሀይማኖት ሳይንስ ነበር፡፡ የሳይንስ ትምህርችን መውደቅ ሀይማኖት እንደመካድ ነው፡፡ በቤቱ ጣራ ስር አያስኖረንም፡፡ ስለዚህ በተቻለን መጠን ሂሳብን ጥሩ ለማምጣት እንታትር ነበር፡፡ በአባታችን ፊት እኔ እና ወንድሜ እንደ ሳይንስ ዲያቆን ሆነን እናገለግላለን፡፡ እናታችን ስትኖር ግን ሳይንስን እንከዳለን፡፡ የእናታችን ሃይማኖት የካቶሊክ ክርስትና ነው፡፡ ዋናው ነገር ማታ ማታ ተንበርክኮ በመፀለይ ይከናወናል፡፡ የእናታችን ሃይማኖት እንደ አባታችን ሃይማኖት ፈተና የለውም፡፡ በሰርተፍኬታችን ላይ ለፀሎታችን ያገኘነው ወጤት ተመዝግቦ አይታይም፡፡ ስለዚህ በማስመሰል እንወጣዋለን፡፡ እሁድ  ከእናታችን ጋር ቤተክርስቲያን ስንሄድ የቅዳሴውን ሰአት በማስመሰል እናሳልፋለን፡፡ ተንበርከኩ ስንባል እንንበረከካለን…ቁሙ ሲባል እንቆማለን፡፡ የተመሰጥን እንመስላለን፡፡ አለመመሰጣችንን ቄሱም ሆነ እናቴ አያውቁም፡፡ ሳይንስ ላይ ግን ተመስጦ ስናጣ የፈተናው ወጤት ላይ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡
 ውጤቱ ኩርኩም ያስከትላል፡፡ በዚህ በተለያየ ሀይማኖት ውስጥ በአንድ ቤት ጥላ ስር ነው እኔ እና ታላቅ ወንድሜ ያደግነው፡፡ አባቴ እና እናቴ ናቸው ያሳደጉን፡፡ የእነሱ ሃይማኖት በእኛ ላይ እንጂ በእነሱ ትዳር መሀል አንድም እክል ሲፈጥር ተመልክተን አናውቅም፡፡ አባቴ ሳይንስ ሲያስጠናን፣ እናቴ ባሏን ተው! ብላው አታውቅም፡፡ እናቴ አንበርክካ ስታስፀልየን…አባቴ ጣልቃ አይገባም፡፡ እሁድ ቤተክርስቲያን አንጠልጥላ ስትወስደን…ሳይንሳዊ አምልኮው ውስጥ ሊያግተን የሚፈልገው አባቴ፤ አንድም ተቃውሞ አያሰማም፡፡ እንዲያውም…መኪናውን ለእሷ ተግባር ይሰጣል- እኛን አድርሶ እሱ ደጀ ሰላሙን እንዳይረግጥ ተጠንቅቆ ወደ ቤት ወይንም ቤተ ሙከራው ይፈተለካል፡፡ በዚህ ግንኙነት ከልጅነት እስከ እድገት አብረን ዘልቀናል፡፡ “Ace” የጐረቤታችን ልጅ ሀይማኖት ላይ ያለው አቋም ምን እንደሆነ አይታወቅም ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ የምን ሀይማኖት ተከታይ እንደሆኑ ገልፆልን አያውቅም፡፡ እኛ ቤት ሲመጣ የእኛ ቤተሰብ ሃይማኖት ተከታይ ይሆናል፡፡ ሳይንስን ከእኛ እኩል ያጠናል፡፡ ከእኛ በላይ ፈተናውን ይደፍናል፡፡ ቤተ-ካቶሊክ ከእኛ እኩል እሁድ እሁድ ይሳተፋል፡፡ ምናልባት ከእኛ የበለጠ ሳያስመስልም አይቀርም፡፡ ግን የ ኤስ ነገር በጣም ማስመሰሉ ሲሰለቸው በጣም አማኝም ሆኖ ሊቀለበስ ይችላል፡፡ በልጅነታችን ወቅት በቤተክርስቲያን ተሞክሮአችን የተከሰተ አንድ ትዝ የሚለኝ አጋጣሚ ነበር፡፡ የካቶሊክ እምነት አማኞች ለአቅመ አማኝ መድረሳቸው የሚረጋገጠው ቁርባን ከወሰዱ በኋላ ነው፡፡ ቁርባን ለመውሰድ ደግሞ ዝግጅቶች አሉ፡፡ ትምህርተ ክርስቲያን መማር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ አንዱ ክረምት (ከሶስተኛ ክፍል ወደ አራት ለማለፍ ስንዘጋጅ) ለቁርባን ትምህርት በቤተክርስቲያኗ ግቢ ከረምን፡፡ እኔ፣ ታላቅ ወንድሜ እና ኤስ አንድ ላይ፡፡ ትምህርቱ በአብዛኛው በመሸምደድ የሚከናወን ነው፡፡ የሸመደድንነውን ስለማወቃችን…ያወቅነውን ደግሞ ስለመረዳታችን የፈተነን የለም፡፡
ሽምደዳው ስለ እግዜር ነው፤ ሽምደዳው በጥያቄና መልስ መልክ በአንዲት ትንሽ መፅሐፍ ተደርጐ በነፍስ ወከፍ ታደለን፡፡ ኤስ ሸምድዶ የጨረሰው ገና ትምህርት ሳንጀምር ነው፡፡ ቄሱ በፍጥነቱ አልተደሰቱበትም፡፡ ኤስ መደነቅ ፈልጐ አይደለም፣ ለፈተና ዝግጁ ስለመሆኑ ለቄሱ   የገለፀላቸው…ወደሚቀጥለው ፈተና ለማለፍ ሲል ነው፡፡
ማን ፈጠረህ?
እግዚአብሔር
ለምን ፈጠረህ?
እንድታምነው እንድታውቀው፣ ትዕዛዙንም ፈፅመህ መንግስተ ሰማያት እንድንገባ ፈጠረን
ስላሴ ስንት ናቸው?
ሦስት
ቄሱ ተሳስተሀል አሉት “አንድም ሶስትም ናቸው ተሳስተሃል - ትምህርት ሳይጀመር ፈትኑኝ ማለት ይኼ ነው ችግሩ…አትቸኩል!” ብለው አሰናበቱት፡፡ ኤስ ግን መጨረሱን አምኗል፡፡ እናም እኛ ትምህርቱን ስንከታተል፣ ትምህርተ ክርስቲያኑን ስናነበንብ እሱ ሌላ ነገር ነበር በደብተሩ ላይ የሚለቀልቀው፡፡ አንድ ቀን ደብተሩን ሲያሳየን ስዕል ሳይሆን ፅሁፍ ሞልቶበት አገኘን፡፡ ምን እየፃፈ እንደሆነ ጠየቅነው፡፡ ድርሰት ነው አለን፡፡ ክርስትና አትማርም ወይ? ስለው…ጨረስኩ አለኝ፡፡ እኛ እሱ የደረሰበት ለመድረስ ሽምደዳችንን ሌት ተቀን አደረግነው፡፡ በልጅነታችንም ቢሆን አንዱን ሳንጨርስ ሌላውን መጨበጥ አንወድም ነበር፡፡ …እሱ የሚፅፈውን ነገር ለመረዳት እኛ የያዝነውን፣ እሱ ተረድቶ ያለፈውን ማጠናቀቅ ግድ ነበር፡፡ እሱም መፃፉን ቀጠለ፤ እኛም መሸምደዳችንን፡፡ ሸምድደን ስንጨርስ ምንም ጊዜ አልተረፈንም፡፡ ቁርባን ደረሰብን፡፡ ከቁርባኑ በፊት ሁለት ስነ - ሥርዓቶች አሉ፡፡ አንዱ የትምህርተ ክርስቲያኑ ትምህርት ዘልቆን እንደሆነ ለማወቅ ተፈተንን፡፡ ሁላችንም አለፍን፡፡ ትምህርቱ ዘልቆን ሳይሆን ጥርሳችንን ነክሰን ስለሸመደድን ነው፡፡ ኤስ ከእኛ የሚለየው ሲሸመደድ እንደ ፎቶ ኮፒ ማሽን በጭንቅላቱ እንዳይረሳ አድርጐ በመንቀስ ነው፡፡ የኛ መሸምደድ ለሱ እውቀት ነው፡፡ ተፈተንን፤ ሁላችንም አንድ ላይ አለፍን፡፡ ለኑዛዜ ቀረብን፡፡ ኑዛዜ ሀጢአትን መናገር ማለት መሆኑ ተነገረን፡፡ ለቄሱ ጆሮ የምንናገረው ሀጢአት በቄሱ ጆሮ በኩል ወደ እግዜር ጆሮ እንደሚቀዳ ተገለፀልን፡፡ የእኛ እድሜ በዚያ ወቅት እንጭጭ ስለነበር፣ ሀጢአታችንን ላናውቀው እንደምንችል ቄሱ አስረዱን፡፡ በመሆኑም ኑዛዜያችን በቄሱ ጥያቄ እየተመራ፣ እኛ በመልስ የተደበቀ ሃጢአታችንን እንድንዘረግፍ ሆንን፡፡ በመሠረቱ ከኤስ በስተቀር ሌሎቹ ልጆች አንድ አቋም ይዘን ነው ወደ መናዘዣ ክፍሉ የገባነው፡፡ “ቄሱ ለሚጠይቁን ጥያቄ ሁሉ መልሳችን “አዎ” የሚል ይሆናል” ተባብለን ተስማምተናል፡፡
የተጠየቅነው ጥያቄ ተመሳሳይ እንደነበር፣ ከኑዛዜው ክፍል ከወጣን በኋላ እርስ በራሳችን አመሳከርነው፡፡ ቄሱ እያንዳንዱን ልጅ ለየብቻው እያስገቡ - ለማንም በማይሰማ ሹክሹክታ ይጠይቁታል፡፡ ተጠየቅን - ተራ በተራ፡፡ ተመሳሳይ መልስ ተራ በተራ መለስን፡፡
ዋሽተሀል?
አዎ
ሰርቀሃል?
አዎ
የቤተሰብ ምክር ችላ ብለሀል?
አዎ (ችላ የምትለዋን ቃል ትርጉም         ማናችንም አናውቃትም፤ በዛ እድሜ)
ተሳድበሀል?
አዎ
ዝሙት ፈፅመሀል?
አዎ (ዝሙት የሚል ቃልም ትርጉሙ         አይታወቅም)
ገድለሀል?
አዎ
ክርስቶስን ክደሀል?
አዎ
ለዚህ ሁሉ ሀጢአታችን የሚሆን ቁጥሩ በዛ ያለ “አባታችን ሆይ” እና “ሰላም ለኪ” ለእያንዳንዳችን ታዘዘልን (ተፈረደብን)፡፡ በመደዳ ተደርድረን የቤተ መቅደሱን ወንበሮች ተቆጣጥረን ቀጠልን፡፡ ፀሎትም እንደ ትምህርቱ በማነብነብ የሚከናወን ነው ያኔ፡፡ከሁላችንም መጨረሻ ወደ መናዘዣ ክፍሉ የገባው ኤስ ነበር፡፡ መጨረሻ የገባው እሱ ቢሆንም ፀሎት ጨርሰን ስንዝናናም ኑዛዜውን ጨርሶ አልወጣም፡፡ ቄሱ ዝግ ባለ ድምፅ ከሚናገሩበት አንዳንዴ ጮክ ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ የኤስ ድምፅ ግን አይሰማም፡፡ ምናልባት ሰይጣን አግኝተውበት ሊሆን ይችላል ብለን መፍራታችን አሁን ትዝ ይለኛል፡፡ ብዙ ቆይቶ ወጣ፡፡ የድርሰት ደብተሩን በአንድ እጁ ይዟል፡፡ ትንሽ የተረበሸ ይመስላል፡፡ የተረበሸ ፊት ሲያሳይ ሆዱን የቆረጠው ይመስላል፡፡ (በልጅነታችን እንደ ሆድ ቁርጠት በተደጋጋሚ የሚያሰቃየን በሽታ አልነበረም) ኤስ ወደ እኛ እያዘገመ፣ ቄሱ ከእንጨቷ ሳጥን (ክፍል) በሩን በርግደው ከኋላ እያስተዋሉት መሆኑ ለሱ አልተሰማውም፡፡ እኔ ግን እይታቸው ዛሬም ትዝ ይለኛል፡፡ እንደማይወዱት ያስታውቅባቸዋል፡፡ መነፅራቸውን ወደ አፍንጫቸው ጫፍ ዝቅ አድርገዋታል፡፡ ኤስን እየተመለከቱት የነበረው ግን በመነፅራቸው ሳይሆን በአይናቸው ነበር፡፡ እርስ በርስ ስለ ኑዛዜያችን ተጠያየቅን…አንዱ የተጠየቀው ጥያቄ ሌላኛው አምልጦት ከሆነ በሚል ሳይሆን አይቀርም፡፡ መልስ እና ጥያቄያችንን አወራርደን አንድ አይነት መሆኑን አረጋገጥን፡፡ አንድ አይነት ሀጢያት ፈፅመን አንድ አይነት ማርከሻ ነው የታዘዘልን፡፡ ከኤስ በስተቀር፡፡
ኤስም እንደኛው መስሎን ነበር፡፡ እኛ መሀል የተለየ ልጅ ቢሆንም በእግዚአብሔር ቤት  መቼም አጉል ልፍጠን አይልም ብለን ነበር የገመትነው፡፡ ግን ይሄ የኛ ግምት ነው፡፡
ሰው ገድለሀል ሲሉህ ምን አልክ             (አልነው)
ገድያለሁ
እኛም እንደዚያ ነው ያልነው?
እናንተ መቼ ነው ሰው ገድላችሁ             የምታውቁት?
አንተስ መቼ ገድለህ ታውቃለህ?
ከዚያ ማስረዳት ጀመረ፡፡ በሚፅፈው ልብወለድ ላይ ገፀባህሪው (አሁን ስሙን ዘንግቼዋለሁ) የሚስቱን አባት እንደሚገድል ነገረን፡ እኔ የገደልኩት የፈጠርኩትን ገፀ ባህርይ ነው፤ እናንተ ማንን ነው የገደላችሁት?ሳታውቁ የሰራችሁት ሀጢአት ሊኖር ስለሚችል …ማጥፋታችሁ ትዝ የማይላችሁንም አጥፍቻለሁ ማለት በእግዚአብሔር ፊት ያስወድዳል ብለው አስተምረውናል፡፡ (አልነው መሰለኝ)
እኔም እኮ (የገፀ ባህርይውን) ሚስት አባት አልገደልኩም፤ የገደለውማ ገፀ ባህርዬ ነው፡፡ ግን እኔ ገድያታለሁ ስል ሳላውቀው በምፅፍበት ጊዜ ለግድያው የተወሰነ አስተዋጽኦ አድርጌ ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡
ለቄሱ እንደዚህ አልካቸው?
አዎ…ግን አባ ተቆጡ፡፡ ብዙ ተከራከርን፡፡ እመን ሲሉኝ አላምን አልኳቸው፡፡ ሰይጣን አሉኝ..ተሳደቡ አልኳቸው…አልተሳደብኩም አሉ፡፡ ተሳድበህ ታውቃለህ ወይ አሉኝ …አዎ አልኳቸው…ተሳድበው ያውቃሉ ወይ ስላቸው በፍፁም አሉ፡፡ …እና እንደዚህ እያልን ብዙ ተጨቃጨቅን፡፡ በደንብ ሳያናዝዙኝ ቀሩ፡፡ ለተናዘዝኳቸው ሀጢአቶችም ፍትሀት አልሰጥ አሉኝ፡፡ ምናልባት አትቆርብም ብለው ሊከለክሉኝም ይችላሉ፡፡ ስለ ኤስ ሳስብ ሰይጣን ይሆን? ወይንስ መልአክ? የሚለው ጥያቄ እድሜ ልክ እልባት የሚያገኝ አይመስለኝም፡፡   


Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 20 December 2014 12:57

“እናትክን በሉልኝ!”

የገሞራው መልእክት፤)
“ለፈፀመው ደባ፣ ለሰራውም ግፉ፣
እናትክን በሉልኝ በዚያ የምታልፉ”

    ገሞራው /ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ/ ኪነትንና የኪነጥበብ ቤተሰቦችን በሚያሳዝን ሁኔታ በሞት የተለየ ብርቅ ባለቅኔ ነበር፡፡ በህይወት በቆየባቸው ዘመናት ሁሉ ብዙ ነገር ታዝቦ፣ የታዘበውንም በብዕሩ ሰቅስቆ የማድማት ልዩ ተሰጥኦ የነበረው ገጣሚ ነው፡፡ ገሞራው የተፈጥሮንም ሆነ ሰው ሰራሽ ህግጋትን አጥብቆ ይሞግት፣ ልዩ ሃብቱ በሆነው የግጥም ኃይሉ ይፋለም የነበረ ጽኑዕ ደራሲ ነው፡
“በረከተ መርገም” በሚለው ግጥሙ ዝናን ብቻ ሳይሆን ፍዳን የተቀበለው ገሞራው፣ የሚታወቀው እጅግ ረጃጅም በሆኑ ግጥሞቹ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ገሞራውን ልዩ የሚያደርጉት መለያዎችም ነበሩት፤ አገሩን ከነፍሱ በላይ ይወድ ነበር፡፡ መንግሥታት ሁሉ አይጥሙትም፡፡ ለገሞራው መንግሥት ማለት በህዝብ ላይ የወደቀ አላል ማለት ነው፡፡ ገሞራው የዓለም ድሆች ሁሉ ጠበቃ ነበር፤ ለድሆች የማይበጁ ከሆነ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ ህግና ዳኝነት፣ ጥበብና ጠቢባን ገደል ቢገቡ፤ ጅሃነም ቢወርዱ፣ ወደ አዘቅት ቢወረወሩ ጉዳዩ አልነበረም፡፡
በገሞራው እምነት ጥበቡ ሁሉ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች በመላ ለድሃ ጥቅም መዋል አለባቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ወንዞች፣ አየሩ፣ ባህሩ፣ ሜዳውና ሸንተረሩ ሁሉ ለድሃ ጥቅም ሊውሉ ይገባል፡፡ አለዚያ የእርግማን በረዶውን ያዘንብባቸዋል፡፡ “እናትክን በሉልኝ!” በሚል ርዕስ 132 ገፅ የፈጀ ግጥሙን የጻፈውም ዓባይን ለመውቀስ ነው፡፡
ግን ዓባይን የወለደችው የዓባይ እናት ማን ናት? እናት ከሌለውስ እንዴት “እናትክን በሉልኝ!” ተብሎ ይሰደባል? ለነገሩ እናቱ እንጂ እሱንማ ምን ብሎ ይሰድበዋል? ገሞራው የስድብ ሱስ የለበትም፤ ግን ሁሉም ነገር ለድሃ ጥቅም ካልሰጠ የእርግማን ናዳውን ያወርድበታል፡፡
“ይንፏፏል ይሉኛል፣ ማንሔ ያንፏፏው፤
ውሃ ጠምቶት ሲረግፍ ወገኔ ያ ሁል ሰው፤
ሀገሩን ቆራርጦ ለባዕድ የሚወርደው፣
ያ ዐባይ የሚሉት የወንዝ ምናምንቴው!
ይንሿሿል ይሉኛል አማቱን ያንሻሻው፤
ውሃ ውሃ እያለ ወገኔን እያየው፣
ባጠገቡ ገፍቶ ያ ዐባይ ሲሸሸው፣
ያ ዐባይ የሚሉት ወንዛችን ከሃዲው!” በማለት የስድብ ዶፉን ያዘንብበታል፡፡
መጽሐፉ የታተመው እ.ኤ.አ በ1981 ስዊድን ውስጥ ነው፤ ገሞራው ዐባይን እንደ ሰው በአካል ቢያገኘው ጥቂት ርህራሄ የሚያደርግለት አይመስልም፡፡ “ወገኔ በውሃ ጥም ሲያልቅ አንተ ለባዕዳን ለመድረስ ነፍስህ እስኪጠፋ ትጣደፋለህ” ነው የግጥሙ ዋና የትዝብት ጭብጥ፡፡
“ደርቡሽን ሲያጣላ የኖረ ከሐበሽ፣
አይደለም ወይ ዐባይ የነበር ሲረብሽ!!
አይደለም ወይ ዐባይ ሠራዊት ያስፈጀ?
ከሺ ዘመን በላይ ሲያታግል ያስረጀ፡፡
አይደለም ወይ አባይ ራስ ያስቆረጠ፣
ንጉሠ ኢትዮጵያን ጐራዴ ያስዋጠ፡፡
አይደለም ወይ ዐባይ በጦር ሲያከሳክስ፣
ቱርኮችን ከደርቡሽ የኖረ ሲያጣቅስ፡፡
በኢርቱዕ መንገድ የወገን ደም ሲያፈስ፣
ዘለዓለም የኖረ እስከ ዛሬ ድረስ፡፡
ስንቱ ነፍጠኛ ነው ኢትዮጵያዊ ሞረሽ፣
ለሀገሩ ብሎ ያለቀው በደርቡሽ?
ኢርቱዕ መነሻ እየሆነ ዐባይ፣
በሃይማኖት ሲያፋጅ የኖረ አይደለም ወይ?
*    *    *
ለማጋደል ተግባር ከሆነ ያንተ መኖር፣
ለምንድን ነው ከቶ የህላዌህ ምሥጢር፣
ክችች፣ ክርር አርጐህ ደርቀኸው የማትቀር?”
ሲል ዐባይን ከአፉ ሳይሆን ከንፁህ ልቡ ያወግዘዋል፣ ይረግመዋል፡፡ እንደ ገሞራው እምነት፤ ዐባይ ለአገራችን ህዝብ የፈየደው ቁምነገር ቢኖር ከተራው ዜጋ እስከ ንጉሠነገሥቱ እንደ ጭዳ በግ ለዕርድ ከማብቃት የዘለለ ዕርባና የለውም፡፡ ዐባይ በሃይማኖት ሰበብ ብዙ ምስኪን ነፍሳት የተቀጠፉበት፣ ዕልፍ ጀግኖች አንገታቸውን ለጐራዴ፣ ደረታቸውን ለጥይት የገበሩበት ትልቅ ጣኦት ነው፡፡
“ኧረ ሰዎች በሉ፣ ድረስ ነፊ ወንፊት፣
ሀገሩ ተዝቆ ተንዶ ሳይሸፍት፣
ዶማና አካፋ ያ አባይ ሆኖበት፣
እንደቡልዶዘርም ነድሎ ገፎ ወስዶት፣
ራቁቱን ሳይቀር፣ አባይ ተወን በሉት፤
ሀገር ባዶ ሳይሆን አፈር አልባ ግተት፣
አፈሩን ማጋዙን ቢተወው ምናልባት”
ከዚህ በላይ ያሉት ስንኞች “መገደብ ባይቻል እንኳ አፈሩን በወንፊት እየነፉ የሚያስቀሩ ብልሆች ያስፈልጉናል፤ አለዚያ አፈሩ እንደሰው ሸፍቶ በረሃ ይገባና መመለሳቸው ያስቸግራል” የሚል የማስጠንቀቂያ ደወሎች ናቸው፡፡
“በቆላው ሀገር ውስጥ ለሚቧርቅ ፈረስ፣
በታችኛው ምድር ለሚፈነጭ ፈረስ፤
እጓዳ ዠማ ውሃ በመስክ ለሚደንስ፣
ልጓሙ ደጋ ነው ከያዙት የማይፈስ” ሲልም ዐባይን መያዝ፣ መቆጣጠር የሚቻለው ከላይ ከደጋው፣ ከምንጩ አካባቢ እንጂ ጉልበቱን እያፈረጠመ ወደ ቆላው ወይም ወደ ጥልቅ ሸለቆ ከደረሰ በኋላ ለመያዝም ሆነ ለመግታት እንደማይቻል አስገንዝቦናል፡፡
ገሞራው ለረጃጅም ግጥሞቹ አዝማች ያበጅላቸዋል፤ ልክ ብዙ ሠራዊት ያለው ኃይል አዝማች እንደሚያስፈልገው መሆኑ ነው፡፡ የ “እናትክን በሉልኝ”  አዝማችም እንዲህ የሚል ነው፡-
“ይፈስሳል ይሉኛል አባይ ዐይኑ ይፍሰስ፤
ያን ስንቱን ወገኔን የውሃ እጦት ሲያምስ፣
የድርቀት ጋንጩራ ሲበላ ስንቱን ነፍስ፤
ውሃ ውሃ እያለ ለጋው ሲቀነጠስ፣
ናይል አባያችን አለ፤ ነበር ሲፈስስ፡፡
ለፈጸመው ደባ፣ ለሰራውም ግፉ፣
እናትክን በሉልኝ በዚያ የምታልፉ”
ገሞራው ለአገሩ ባዳ ሆኖ በስደት ከሚኖርበት ሀገረ ስዊድን የወገኑን በረሃብ መማቀቅ፣ በጠኔ መውደቅ በመገናኛ ብዙኃን ሲሰማ ልቡ ክፉኛ ደማ፡፡ የሚያደርገው ቢያጣ ለምስኪን ወገኖቹ ዳቦ መስጠት ባይችል፤ ተፈጥሮን በተለይ ዐባይን መስደብ የቁጭቱ መወጫ አድርጎ ወሰደው፡፡
“... እናትክን በሉኝ!” ሲልም በመልእክት ዘለፈው፡፡
“ዓይኑ ይፍሰስና እዩት አባይ ሲፈስ፣
እንደ ቀትር እባብ ሲነጉድ፣ ሲርመሰመስ፣
ላልተወለደበት ችሮታ ሊለግስ፣
ያ ስንቱ ወገኑ በጥማት ሲታመስ፤
ድረስና አርጥበኝ እያለው ስለነፍስ፣
እንዲያ ሲለምነው፣ እሪ ሲል ቢመለስ”
ገሞራው በዐባይ ላይ ያለው ጥላቻ ማብቂያ ያለው አይመስልም፡፡ ዐባይ ብቻ ሳይሆን ሐይቆችና ሌሎች በዓለም ያሉ ወንዞች ሁሉ ለድሃ ካልጠቀሙ፣ ድርቅን መከላከል ካላስቻሉ ከንቱ ፍጥረታት መሆናቸውንም በምሬት ይገልፃል፡፡
ለምሳሰሌ ከተሰጣጠቀ መሬት ፎቶግራፍ ሥር እንዲህ በሚል ግጥሙ የልቡን ተንፍሷል፡-
“ምድሪቱን ተመልከት፣ አፏን ከፍታ ስትጮህ፣
ዋይ ዋይ ድረስልኝ እያለች ተማጥናህ፣
እያለች ወዳንተ ኧረ የውሃ ያለህ፣
በደረቅ ጉሮሮ፣ እሪ ስትል ምድርህ፣
ምን ይሆን ያ ጆሮህ መስማት የተሳነህ?”
* * *
… ወገን ሲያልቅ በድርቀት ውሃዋን ካልሰጠች፣
ምድረ ሐይቅ በመላ ለምን ተፈጠረች?
ለምንስ ዓላማ እንዲያ ትኖራለች?”
ገሞራው ዐባይን ብቻ አይደለም “እናትክን በሉልኝ!” የሚል፤ ሃይቆችን ሁሉ ያወግዛል፡፡ “ምድረ ሐይቅ በመላ ለምን ተፈጠረች?” ሲል የወንዞችን፣ የሃይቆችንና ኩሬዎችን ጥንተ ተፈጥሮ ጭምር ያለመታከት ይጠይቃል፡፡ ብሎት ብሎት አቅም ሲያጣ ወደ ተለመደው እርግማኑ ይገባል፤ እንዲህ እያለ፡-
“ቀድተህ አፍስልኝ በፅዋ፣ በገንቦ.
ዋጋውን ስጥልኝ በሚካኤል፣ ባቦ፡፡
የሚቻልም ቢሆን እርጭና ያን ቤንዚን.
በእሳት አቃጥልልኝ ተኮማትራ እስክትበን፤
ድብን፣ ጭርር ብላ ትቅመሰው ድርቀትን፡፡
አደራ አቃጥልልኝ፣ እንደደላት አትቅር፤
ወገኔ እንዲያ አልቆ እሷ ተዝናንታ አትኑር፡፡
           *  *  *
እስከዚያው ድረስ ግን ስድቤን አድርስልኝ፣.
ለሰራችው ወንጀል ዋጋዋን ስጥልኝ፤
ከተኛሽበት ላይ ያድርቅሽ በልልኝ”
ገሞራው የወገኑ በድርቅ መሰቃየት እንጀቱን ዘልቆ አንገብግቦታል፡፡ ረሃቡ ይሞረሙረዋል፤ ጥሙ ያቃጥለዋል፡፡ በአውሮፓ የሚኖር ቢሆንም የሀገሩን ዜጎች ስቃይ ይሰቃያል፤ ያስብ ያስብና አማራጭ ሲያጣ ውሃውን መራገም ይጀምራል “ያቃጥልህ፣ ያኮማትርህ ወዘተ” እያለ የስድብ ናዳውን ያዥጎደጉዳል፤ ርግማን የወገንን ጠኔ ያስታግስ፣ የችግር ድውያንን ይፈውስ ይመስል፡፡
ገሞራው ለወራጅ ውሃ ሁሉ ወህኒ ቤቱ መስኖ ነው ብሎ ያምናል፤
“ወንጀለኛ ውሃን ሥርዓት ካላሰረው፣
ብዙ የሚያጠፋ ባለጌ ዋልጌ ነው፤
በጣም አደገኛ አድርቆ ገዳይ ሰው!!
ማረሚያው እስር ቤት ለመረን ልቅ ውሃ፣
አንድ‘ኮ መስኖ ነው አርጣቢ በረሐ፡፡
ታዲያ‘ኮ ለምን ነው ዐባይ ያልታገረ፣
በመስኖው እስር ቤት ሳይገባ የቀረ፣
በዋልጌነት ግብሩ ሲቃበጥ የኖረ?”
ገሞራው ይጠይቃል፤ ግን መልስ አያገኝም፡፡ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ ሲያጣም እርግማኑን ይቀጥላል፡፡
“ይፈስሳል ይሉኛል  ያ ዐባይ ትልቁ፣
ዓይን ካለው ይፍሰስ፤ ይውጣ ውልቅልቁ፤
ወገኖች ካልረዳ በውሃ ጥም ሲያልቁ!
እመትርህ ነበረ ቁርጥርጥ አድርጌ፣
በመስኖ ጎራዴ ከራስጌ ከግርጌ፤
ከውሃህ መንፈግህ ነህና ባለጌ”
ከእርግማኑ በኋላ የቦታም የአቅምም ርቀት እንዳለ ሲገነዘብ ገሞራው የሚከተለውን ብሏል፡-
“ግና ምን ያደርጋል፤ አንተ ወዲያ ማዶ
እኔ ደግሞ ወዲህ እቅድ ተወላግዶ፣
ለጊዜው ድነሃል አወይ እኔ ነዶ!”
ገሞራው ይህን ቁጭትና ርግማን የተሞላበት ግጥም ያሳተመው በ1981 ነው፤ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የዐባይ ግድብ መጀመሩን ሲሰማ ምን ብሎ ይሆን? ምን አይነት ስሜትስ አድሮበት ይሆን? ስሜቱን በወጉ ሳንረዳለት ድንገት አለፈ፡፡



Published in ጥበብ

በጋዜጠኛ ግዛቸው እሸቱ ላይ ባደረሰው ድብደባ ተከላከል ተብሏል

“ፋየር ፕሩፍ” የተሰኘውን የእንግሊዝኛ ፊልም ወደ አማርኛ መልሶ ከወ/ሮ ቤተልሄም አበበ ጋር ለመስራት ከተስማማ በኋላ ብር ተቀብሎ ፊልም ባለመስራቱ ብሩን እንዲመልስላቸው በመጠየቃቸው፣ ሳይወዱና ሳይፈቅዱ የቀረፀውን  ድምፅና ምስላቸውን ለባለቤታቸው እንደሚሰጥ በማስፈራራት ወንጀል ፈጽሟል በሚል ክስ የቀረበበት አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፤ ጉዳዩ በወንጀል አያስጠይቀውም ሲል ፍ/ቤት ውሳኔ ሰጠ፡፡ ፍ/ቤቱ፤ ለፊልም የወሰደውን ብር ባለመመለሱ መጠየቅ ካለበት በፍትሃብሄር እንጂ ወንጀል ለመፈፀሙ የሚያመላክት መረጃ እንደሌለ በውሳኔ መዝገቡ ላይ ጠቁሟል፡፡ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ስሜን አጥፍተሃል በሚል በጋዜጠኛ ግዛቸው እሸቱ ላይ ድብደባ ፈፅሟል በሚል በቀረበበት ክስ ፍ/ቤት  እንዲከላከል የወሰነ ሲሆን ተከሳሽ መከላከያውን እንዲያቀርብ ለጥር 5  ቀጠሮ ተይዟል፡፡
በነሐሴ ወር 2005 ዓ.ም ውስጥ የግል ተበዳይ ወ/ሮ ቤተልሔም አበበና ተከሳሹ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ “ፋየር ፕሩፍ” የተሰኘውን የእንግሊዝኛ ፊልም ወደ አማርኛ ለመመለስ ተነጋግረው፣ ከሳሽ በተለያዩ ጊዜያት 470 ሺህ ብር በተከሳሽ የባንክ ሂሳብ ውስጥ ማስገባታቸውንና ፊልሙ ሳይሰራ ስድስት ወር ስላለፈው ገንዘቡን እንዲመልስላቸው በጠየቁት ጊዜ ያለፍላጎታቸው ከሰው ጋር ሲሳሳሙ ቪዲዮ በመቅረፅ “ገንዘቡን ከጠየቅሽኝ ይህን ቪዲዮ ለባለቤትሽ እሰጣለሁ” በማለት በማስፈራራቱ በፈፀመው ወንጀል መከሰሱ ይታወሳል፡፡
ተከሳሽም ለፊልሙ ስራ 150 ሺህ ብር በባንክ ሂሳቡ መግባቱንና ከዚያ በኋላ ተከሳሽ ከአንድ ታዋቂ አርቲስት ጋር ለመዝናናት በተለያዩ ጊዜያት ብሩን እንዲያመጣላት እየላከችው እያወጣ ሲሰጣት ብሩ ማለቁንና ምንም አይነት ገንዘብ እሱ ዘንድ ጋ እንዳልቀረ በመግለፅ፣ “ከዚህ በኋላ ብሩን ከጠየቅሽኝ ለምንና መቼ እንዳጠፋሽው የድምፅ ማስረጃ ስላለኝ ለባለቤትሽ እሰጥና እውነቱ ይወጣል” ብሎ ስለመናገሩ ለፍ/ቤት ማስረዳቱን የውሳኔ መዝገቡ ያስረዳል፡፡ ፍ/ቤቱ የተበዳይና የተከሳሽን አቤቱታ ምላሽና የቀረቡትን ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ ተከሳሽ የተከሰሰበት ጉዳይ በወንጀል እንደማያስጠይቀው ገልፆ ተከሳሽ ለፊልሙ ስራ በሚል ገንዘብ ተቀብሎ አልመለሰም የተባለው ጉዳይ መታየት ያለበት በፍትሃ ብሄር ህግ እንጂ የወንጀል ኃላፊነት የሚያስከትል አይደለም” በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በወ/ሮ ቤተልሄም በተመሰረተበት ክስ ወቅት ለፍተሻ ተብለው የተወሰዱበት ሁለት ኮምፒዩተሮች፣ አንድ HP ላፕቶፕ፣ 156 ሲዲዎች፣ በማስረጃነት የተያዘው ቁምነገር መፅሄትና ለዋስትና ያስያዘው ሁለት ሺህ ብር እንዲመለስለት ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡  

Published in ጥበብ

[የካሜራዋ ሰምና ወርቅ “የሜሊ ታደሰ” የእናትና ልጅ ዉብ መሳጭ ፎቶ ግጥሙን ይመጥነዋል።]
ካዛንቺስ የአራት ትዉልድ እትብትና ትዝታ ብቻ ሳይሆን የገደል ማሚቶም የተከማቸበት መንደር ነዉ። ይህ ስፍራ -ከመናኸሪያ ከፍ ብሎ- ለደምሰዉ መርሻ የኅላዌና የብዕር ትርታ ቤተመቅደሱ ነዉ። እኛ ከሚዳሰሰዉ እየታከክን ተላምደነዉ ልብ የማንለዉ ይበዛል፤ ደምሰዉ ግን እያደባ “ሽንቁር” እያበጀ በግጥም ይደመማል። በዕዉቀቱ ስዩም “ያጮለቀ ብቻ” ብሎ የተቀኘዉ ለራሱና ለደምሰዉ መርሻ ይመስለኛል።
ጠቢብ ቤት ሳይኖረዉ፥ መስኮት ይከራያል
ግድግዳ ሳያቆም፥ ሽንቁር ይከራያል
ያጮለቀ ብቻ ሁሉን ነገር ያያል። -----
[ስብስብ ግጥሞች፥ ገፅ 102]
ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ “መንገድ ላይ የሚያብረቀርቅ ስንኝ እያፈተለከበት በሰመመን የሚሰፍ አንድ ባለቅኔ ላስተዋዉቅህ” ብሎ ከደምስ ጋር አገጣጠመኝ። ዕዉነትም በወረቀት ያልተፃፈ በቃሉ የጠቀለለዉን ሁለት-ሶስት ግጥም ሲያሰማኝ፥ ለፈንጠዝያ ሣይሆን ዉስጡን ለመዘመዘዉ ትዕይንት ሆነ ግለሰብ ሲጠወልግና ሲፈካ አገኘሁት። አነጋገሩ፥ አተካከዙ፥ ድንገት መጨነቁ፥ ሳትጠብቁት መሳቁ ... እንጀራ በመጠኑ፥ በብዛት ግን ግጥም እየቆረጣጠመ መጐምራቱ ያስታዉቃል። ያኔ፥ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ያስቀረሁት አጭር ግጥም ዛሬም ያባንነኛል። ከወራት በፊት ማርታ ሃይለየሱስ የደምስን ሶስት ግጥሞች facebook ላይ ስታንሳፍፍ መንፈሴ ተረበሸ። ግጥሙን “የድሃ እናት ተስፋ”ን አብረን እናንብብለት።
“ካንዲት ምስኪን ድሃ
ይወለዳል ንጉሥ፥ ይወለዳል ጀግና”
መባሉን ሰምቼ፤
አምና ጀግና ወለድኩ
እራብ እየላሰኝ፥ ችጋር ላይ ተኝቼ፤
ይኸዉ ዘንድሮም አረገዝኩ
ያለመጠራጠር ንጉሥ እንደሚሆን
በምነቴ ፀንቼ።
እናት ድህነቷን ለመቋቋም የተስፋን ዱካ ተከትላ ታዘግማለች መባሉ የተለመደ እሳቦት ስለሆነ በግጥም አይነቃቃም። ግን የተካነ ባለቅኔ ይህን ፍዝነት በመግፈፍ በለጋነት እንዲነዝር ያበቀዋል። እንዴት? ደምሰዉ ሥነተረት በመሰለ ትንቢት ጀመረ። “ሥነተረት -mythology- ... ለተፈጥሮና ለኅብረተሰብ ኃይሎች ዲበ ተፈጥሮአዊ መልክና ፍች በመስጠት በሰዎች ዘንድ ሃይለኛ ስሜቶችን ... የሚቀሰቅስ ነዉ። ... የሃይማኖትን ጥንተ ነገሮች ያቀፈ ቢሆንም ሥነዉበታዊ ፍችም አለዉ። ከሚቀሰቅሳቸዉ ሥነዉበታዊ ስሜቶችና ከሚጠቀምበት ምናባዊ ፈጠራ አንፃር ሥነተረት ንቁ ያልሆነ የእዉነታ የሥነ ጥበባዊ አመለካከት ነዉ” [ማሌመዝገበ ቃላት፥ ገፅ 117] “ካንዲት ምስኪን ድሃ/ ይወለዳል ንጉሥ፥ ይወለዳል ጀግና” ሥነዉበታዊ አቅሙ በምናብ የሆነ ታሪክ፥ የተለየ ድርጊት ለማጥለል ማመቸቱ ነዉ። የሙሴን፥ የኦዲፐስ፥ የሼህ ሁሴን ጅብሪል ... ትንቢትም ይቀሰቅሳል። ለእናት ብቻ ሳይሆን ለሀገር ዕጣና ጦስ የመብቃት ጉልበት። እናት ለዚህ ትንቢት እንደ እመቤታችን የታጨች ይመስል ተንገላታለች። ግጥሙ ወሬ-ዘገባ ሳይሆን የአለመሸነፍን እልህ ለመቀኘት ሣይንዛዛ ቅዠት የመሰለ ትንቢትን በድርጊት ያላትማል።
እጦት ሶስት አይነት ሰዉ ይመለምላል። ኑሮ ገፈታትሮ ጥግ ሲያስገባዉ ተስፋ የሚቆርጥ፤ እጅጉን እየታከተ እየተላተመ መንፈሳዊ ተገን ሳይለማመጥ ለብሩህ ቀን የሚበቃ፤ ያጣ የነጣ፥ የአንድ ቀን ምግብና አዳር ፈተና የሆነበት፥ አንዳች ታዕምር ጨምድዶ የማይለቅ - ናቸዉ። ደምስ የቀረፃት እናት ሶስተኛዋ አይነት ናት፤ በትንቢት አምና ትንቢቱን ለመኖር እየተላጠች፣ ተስፋን እንደ ጥጥ ከምንም ከባዶ የምትከምር ያልጐበጠች እናት። ምኞት አልያም ተስፋ እዉስጧ አድፍጦ፣ ልጇን ወንዝ ልታሻግር ያለ እረፍት ዳክራ፣ ትንሽ ሲቀራት ሞት የሚወስዳት እናት ታስተክዛለች። ሀዲስ -የበዐሉ ግርማ ገፀባህሪ- ለወግ ለማዕረግ ሊበቃ ሲቃረብ እናቱ አሸልበዉ ያልፋሉ።
“እርጅና ከቀን ቀን እየተጫናቸዉ የሚሄዱት ድሃ እናቱ ብቻቸዉን ናቸዉ። ከእሱ ሌላ ምርኩዝና ተስፋ የላቸዉም... ቅጠል ለቅመዉ በመሸጥ ... እህል ቀምሰዉ ማደር ተስኖአቸዋል ... የተለበለበ እንጨት የሚመስለዉ ክንዳቸዉ ተዘርግቶ ጭራሮ መስበር አቅቶታል ... ፀሐይ ወጥታ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ደከመኝን የማያዉቁ ሴት፥ እየበረደ ከሚሄደዉ ምድጃቸዉ ዳር ከቤት መዋል ጀምረዋል። ... ለመኖር የነበራቸዉ እልክ ያለቀ ይመስላል።... የድሃ ህይወት -ረጅም የግዞ ፍታት... እናቱ “ድሀም አገር አለኝ ይላል? መቃብርም የለዉ እቴ። በህይወት የተፋችዉ መሬት ሲሞት ምን መቃብር ትሆነዋለች? ... ካፌ እየነጠኩ የእድር መዋጮዬን ስከፍል የኖርኩት ለምን መሰለህ? ቀባሪ እንዳላጣ ነዉ። ... አይዞህ ድህነትን እንጂ መጥፎ ስምና እዳ አላወርስህም።” [“ሀዲስ” ልቦለድ]
ድህነትን መዉረስ ይጐመዝዛል። ሀዲስ፥ ነብይ መኰንን “ጉስቁልቁል ያለ ሰዉዬ፥ ኑሮ እንደሸሚዝ ያለቀበት” የሚለዉ አይነት ቢሆንም ተስፋዉ አልነጠፈም። ማርክስ “የህዝብ ዕፀፋርስ ሃይማኖት ነዉ” ቢልም፥ ሰዉ እንዳያምፅ መንፈሳዊ ቅዠቱ እግር ተወርች ያስረዋል ቢልም ተደፈጥጦ ከመቅረት የሆነ የተስፋ ጭላንጭል እያደባ  መከተል ይበጃል። ደምሰዉ በግጥሙ ከእናት ሽንፈት ይልቅ በተስፋ የማንሰራራት እልህ ነዉ የተፈታተነዉ። “ልጄ አንድ ቀን ሰዉ ሆኖ ያልፍልኛል” -ወይ ጀግና ወይ ንጉሥ- በየዳሳሳ ጐጆ ሚካኤልን፥ ማርያምን ... የሚማጠኑበት ተስፋ ነዉ። ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ይህን ከመሰለ ተስፋ አንዲት እናት ታዕምር ስታባብል ተቀኝቷል። ሀሩሩ በሚወብቅበት ወር የከሰል ክምር የምትነግድ “ጉሊት የዋለች ነፍስ” ጦሟን ላለማደር ለመንፈሳዊ እርዳታ ታጐበድዳለች።
በወርሀ ግንቦት፥
ገዢ የሌለዉ ከሰል፥
አሁንም አሁንም እየሰፋፈረች፤
እሷ ታስባለች።
አንጋጣ ወደ ሰማይ
(ደመናም ባይታይ)
እግዜር ምን ተስኖት፥
ከጠራዉ ሰማይ ስር፥ ዝናቡን አዉርዶት፤
ሰዉ ሁሉ በርዶት፤
መደቧን ሲከበዉ።
እሷ ትገርማለች፤
በደረቀ ግንቦት፥
ከፈረሰ መደብ፤
ከደቃቅ ከሰል ስር፤ ተስፋ ትምሳለች::----[“እዉነት ማለት” ...፥ ገፅ 20]
ቴዎድሮስ ከምንም አንሰራርቶ ጀግናም ንጉስም ሆነ። የደምሰዉ ድሃ ሴት እሱን ዳግም ለመዉለድ -ያለ ዘመኑና አዉዱ- ትንቢቱን እንደ ትኩስ ቃል ወርሳ ይሆን? በአባቷ ሽንፈት ተማራ ምንትዋብ አንድ ለናቱን ልትሳለቅበት ሞከረች።  
ሺህ ፈረስ ከኋላዉ፥ ሺህ ፈረስ ከፊቱ
ሺህ ብረት ከኋላዉ፥ ሺህ ብረት ከፊቱ
ይህን ሳታይ ሞተች ኮሶ ሻጭ እናቱ።
ደምሰዉ የሴቷን ህልም እንደራሰ ዉስጥ ልብስ፥ እንደ ገመና በየስንኙ ላይ አሰጣዉ እንጂ እናትየዉን አበጅታለች ወይም ተሳስታለች አላለም። ተስፋ ወንዝ ባያሻግራትም እዉስጡ ከመስመጥ ለጊዜዉ ያንሳፍፋት ይሆናል። ግን አንዳንዴ ሰዉ ለመትረፍ ወደ ብርሃን የገሰገሰ እየመሰለዉ የግልብጥ ከጨለማ አዘቅት ይወድቃል። የተሸሸገ ታሪክ አላት። የወለደችዉ ለምትወደዉ መከታ ለሚሆናት ተባዕት ሳለ ከከዳትስ? “አምና ጀግና ወለድኩ/ እራብ እየላሰኝ፥ ችጋር ላይ ተኝቼ፤”ስትል እመጫት እንጀራ በወጥ ማጣቀስ እንዳማራት ለረሃብ ስትዳረግ ይሰቅቃል። አሁን ደግሞ በሌላ አዳም ተመክታ ቁስሏ ሳይጠግ እንደገና ፀነሰች። እንደ ሙሴ ፅላት የምታምነዉ ወንድ ቢያስፈልጋትም መች ሰመረ? ለምን ልቧ ለወንድ ትርክክ አለ? እንዴትስ ተዘናጋች? እነዚህ መልስ ልታገኝባቸዉ ከፊት ለፊቷ የሚርመሰመሱ ጥያቄዎች አይደሉም፤ አንባቢን ነዉ የሚያሳስቡት። እንደ ታማኝ ዉሻ ዝም ብሎ የሆነ ትንቢት ተከትሎ መኖር ተስፋም ነዉ።ዶ/ር አብረሃም ፈለቀ “ባይጣፍጥ ህልማችን” እንዳለዉ ነዉ።
ከሜዳ ላይ ሲቀር - ድካም ልፋታችን
በዉሃ ሲበረዝ - ወዛችን ላባችን ?
በዳዋ ሲወረር - ቡቃያዉ ምርታችን
ምን ይዉጠን ነበር ?
ባይጣፍጥ ህልማችን
ባይጥም ቅዠታችን :: ----
[ቢላዋና ብዕር፥ ገፅ 7]  
ደምሰዉ እንግልቷን ስለአደመቀዉ ባይናገረዉም ከድህነት ለመገላገል ልጅ መገላገል መፍትሔ እንዳልሆነ ይጦቅማል። ከባዶነት፥ ዉስጧ እየተፍገመገመ የሚሰማት እንደ ተስፋ የሚሰፍ የሃሳብ ላባም ቢሆን መከተል መርጣለች። ታገል ሠይፉ “ፈልግ ይታየሃል” በሚል ግጥሙ ከጨለማ እምብርት ብርሃን ቦግ ሲል ሰዉ አስተዉሎ አፈፍ ካላደረገዉ አይነጋለትም ባይ ነዉ።
መብራት ታጠፋና
ቤት ታጨልምና
በጨለማዉ መሐል
ፈልግ ይታይሃል
ከዉስጥ የቆምክበት -የዉስጥ ዓለም ጮራ
አንተ ካንቀላፋህ - ያ መብራት ሲበራ
የለም ሌላ ፀሐይ፥ የለም ሌላ ብርሃን፥                አንተን የሚመራ። ---
[“የሰዶም ፍፃሜ”፥ ገፅ 51]
ጀግና እና ንጉሥ ለምትወልድ ሴት የታያት ተስፋ፥ ከትንቢት የተፈለፈለ እንጂ እንደ መብራትስ የሚመራት አይደለም፤ ድህነት ይበልጥ ዶቀሳት። ዕጣዋ ምን ይቀፈቅፍላታል? ወገግታ ሳይሆን እንደ ሙዝ ልጣጭ የሚያንሸራትታት የማይጠቅም ትንቢት ደምበሾነቱ ያደናግራል። ልጆቿ ለመመገብ፥ ለመልበስ ... ሲደርሱ “እንደ ሰዉ” ለመኖር ታባቃቸዉ ይሆን? ሰዉ ሌጣዉን ቢሆንም እጅ ካጠረዉ ተራ በመሰለ ጥቃቅን ምኞት ዉስጡ ይሸበራል፤ ሥነልቦናዊ እንግልቱ ይደፈርሳል። ደምሰዉ በሌላ “ግማሽ ገደል” ድንቅ ግጥሙ ይህን አስተዉሏል። በዚያ የቀን ግማሽ ጨረቃን እንዳጨ፥ ተጀንኜ ማልፈዉ እንደሰዉ እንደሰዉ እንደሰዉ አለ አይደል አንዳንዴ እንደሰዉ የምታይ እየመሰለኝ ነዉ በዚያች ትንሽ ነፍሴ የምጨማለቀዉ አጨብጭቦ ማዘዝ እየናፈቀኝ ነዉ፡፡ሊገለጥ የሚያዳግት፥ የዕለት ጋጋታና እንቅስቃሴ ዉስጥ፥ ልብ የማይሉት ምኞት... ሳይፈረካከስ ሳይበተን ደምስ በግጥም እሳት ጭሮበት ቦግ ሲያደርገዉ ያጥበረብራል። የድህነት ክፋትና መዘዝ ለፊልምና ለአብይ ልቦለድ የሚትረፈረፍ ጭብጥ ነዉ።
ተስፋን ከነተበ መቀነት ዉስጥ ተሸሽጐ እንደ ሆነ የምር ማበጠር ያባብሰዋል። ይህንን ነዉ ደምሰዉ በእምቅ አጭር ግጥም ሸብሽቦ ማወራጨት የደፈረዉ። ሁሉም ነገር የተሰወረ ስንጥቅ አለዉ፤ ለዚህም ነዉ ብርሃን ሾልኮ የሚያስደምመን ይላል ካናዳዊ ሙዚቀኛ Leonard Cohen “There is a crack in everything. That is how the light gets in”። ትንቢት ደግሞ ዉሸትም ዕዉነትም ነዉ።

Published in ጥበብ

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በንግድ ምልክት፣ በአዕምሮ ፈጠራና በዲዛይን (ንድፍ) ላይ ጥበቃ ለማድረግ በዓለም አቀፉ የአዕምሮ ንብረት ድርጅት (World Intellectual Property Organization) WIPO ትብብር አዲስ የዲጂታል አሰራር መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም በማኑዋል የአዕምሮ ንብረቶችን ይመዘግብና ይቀበል የነበረው መስሪያ ቤቱ፤ ከተባበሩት መንግስታት ስፔሻላይዝድ ድርጅቶች አንዱ በሆነው “ዋይፖ” በተደረገለት ድጋፍ በ2.ሚሊዮን ዶላር የተገዙ ሶፍትዌሮችን፣ ሰርቨሮችን፣ ኮምፒዩተሮችንና ፕሪንተሮችን በማስገባት Intellectual Property Automation System (IPAS) ሲስተምን ይፋ አድርጓል፡፡ በእለቱ የዋይፖ ተወካዮች በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በመገኘት የዘረጉትን ሲስተም ለጋዜጠኞችና ለጽ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች አስጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር ናፍቆት ዮሴፍ፤ በተዘረጋው ሲስተም፣ በጠቀሜታውና በዋይፖ ትብብር ዙሪያ ከጽ/ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

       የተዘረጋው አውቶሜሽን ሲስተም ጠቀሜታው ምንድን ነው?
እንግዲህ የዚህ ሲስተም በአገራችን መዘርጋት ጠቀሜታው በርካታ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው በአዕምሮ ፈጠራ (ፓተንት)፣ በንግድ ምልክትና በዲዛይን (ንድፍ) ባለቤትነት  ጥበቃ ላይ አስተማማኝና ዘለቄታ ያለው ስራን ለመስራት ያስችላል፡፡
 ይህ ሲባል እስከዛሬ አመልካቾች በወረቀት ይዘው የሚመጡት የባለቤትነት ጥያቄ አንድ ጊዜ በዚህ ሲስተም ውስጥ ከገባ ካልተፈለገ የይገባኛል ጥያቄዎች፣ ከመጥፋት ጭቅጭቅና ከመሰል ጉዳዮች ተጠብቆ ይቀመጣል፡፡
ሁለተኛ አመልካቾችን ከጊዜ ብክነትና ከመጉላላት ይጠብቃል፡፡ ባሉበት ሆነው ጉዳያቸውን መከታተል እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ማለት ነው፡፡ አንድ አመልካች ፈጠራውን፣ የንግድ ምልክቱን ወይም ዲዛይኑን ይዞ ሲመጣ ኮድ ይሰጠዋል፤ ፋይል ይከፈትና የፋይሉ ቁጥር ሲስተሙ ውስጥ ይመዘገባል፡፡ ሌላ ጊዜ ሲፈለግ ኮዱን ኮምፒዩተሩ ላይ አስገብቶ  በፍጥነት ለማግኘት ያስችላል፡፡ ይህ ቀልጣፋ አሰራርን ይፈጥራል፡፡ ባለንብረትነትን ያረጋግጣል፡፡ አንድ ምርትም በፓተንት፣ በንግድ ምልክትና በዲዛይን ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ጥቅሞቹ ናቸው፡
ይህን ሲስተም ለመዘርጋትና ስራ ላይ ለማዋል የዓለም አዕምሮ ንብረት ድርጅት “WIPO” ወደ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉ፣ ሰራተኞቹን በራሱ ወጪ እዚህ ድረስ መላኩና ሲስተሙን መዘርጋቱ ተገልጿል፡፡ ይህን ድጋፍ ያደረገው ለምንድን ነው?
የዓለም የአዕምሮ ንብረት ድርጅት ከUN ስፔሸላይዝድ ድርጅቶች አንዱና በአዕምሮ ንብረት ላይ አተኩሮ የሚሰራ ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ያደረገው ይህ ድርጅት፤ በ60 የዓለም አገራትና በ20 የአፍሪካ አገራት ይሰራል፡፡ ድርጅቱ ከሚሰራባቸው የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ ድርጅቱ ሰራተኞቹን ሲልክ ይህ ሶስተኛ ጊዜው ነው፡፡
 ድርጅቱ በተለይ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን ለማገዝ በያዘው ፕሮጀክት፣ ታዳጊ አገሮችን አግዘን የአዕምሮ ንብረት ጥበቃቸውን ማጠናከር አለባቸው ብሎ በማመኑ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ በዚህ መሰረት ሰራተኞችን ወደዚህ ሲልክ፣ የአውሮፕላን ትኬት፣ ሆቴል… ሁሉን ነገር ችሎ ነው፤ ከእኛ የሚጠበቅ ነገር የለም፡፡
በማንኛውም ጊዜ ድጋፍ ስንጠይቅ ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ይህ የድጋፋቸው አንዱ ክፍል ነው፡፡
ሲስተሙን ለመጫን የሚያስፈልጉ ከላይ የጠቀስሻቸውን ንብረቶች ለመግዛት ወደ 2 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርገዋል፡፡ በቀጣይ የቅጅ መብት ላይ ለምንሰራውም ድጋፍ ለማድረግ ሌላ ፕሮጀክት አላቸው፡
ከዚህ በፊት ምን ምን ድጋፎችን አድርገዋል?
እስካሁን ብዙ ፕሮጀክቶችን ሰጥተውናል፡፡ ለምሳሌ የብሔራዊ አዕምሮ ንብረት ፖሊሲ ድራፍት ይደረግ ብለን ጠይቀናቸው፣ አማካሪ በመቅጠር ድጋፍ ስለሰጡን አሁን ድራፍቱ አልቋል፡፡ እስካሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ይህ ፖሊሲ የለም ነበር፤ ሁለት አማካሪ በመቅጠር ጥናቱን ጨርሰዋል፡፡
 በሚቀጥለው ጥር መጨረሻ ላይ ለውይይት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሌላው የአዕምሮ ንብረት አካዳሚ (If Academy) ነው፡፡ ይህንንም ፕሮጀክት ቀርፀን አቅርበን ፈቅደውልናል፡፡ ይህ አካዳሚ በቅርቡ ስልጠናና የማስተርስ ስራ ይጀምራል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የቅጅ መብትን አስመልክቶ የፊልም፣ የሙዚቃና የድርሰት ኢንዱስትሪው እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው እየጠቀመ ያለው ምን ያህል ነው የሚለውን እንዲጠናልን ጠይቀናቸው 70 ሺህ ዶላር አውጥተው አማካሪ ቀጥረውልን እየተጠና ነው፡፡ ጥናቱም የመጨረሻ ሪፖርት ላይ ደርሷል፡፡ እናም ድጋፍ በጠየቅን ቁጥር ፕሮጀክቶችን ይሰጣሉ፡፡ በተለይ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን በጣም ነው የሚያግዙት፡፡
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ተወካዮቹን ሲልክ ለሶስተኛ ጊዜ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት የመጡባቸው ሁለት ምክንያቶች ምን ምን ነበሩ፤ የአሁኑ አመጣጣቸውስ በዋናነት ምን ላይ ያተኩራል?
ከዚህ በፊት ይህንኑ ሲስተም በተመለከተ ስራዎች ነበሯቸው፡፡ አሁን ግን ሶፍትዌሩን ጭነው ባለሙያዎች አሰልጥነውና አስፈላጊውን ነገር አሟልተው፣ ሲሰሙ ስራ ላይ መሆኑን ይፋ ያደረጉበት የመጨረሻ ቀን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የአዕምሮ ፈጠራ የንግድ ምልክትና የዲዛይን ባለቤቶች ሲያመለክቱ፣ በዚህ ሲስተም ነው የሚስተናገዱት ማለት ነው፡፡ በወረቀት የምንቀበልበት አሰራር አብቅቷል፡፡ ይህ አሰራር የመጨረሻ ተጠቃሚ የሚያደርገውም ባለንብረቱን ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ፋይል እየጠፋና እየተበላሸ መጉላላቶች ይደርሱ ነበር፡፡ አሁን ግን የወረቀት ምልልስ ቀርቶ አውቶሜትድ ሲስተም ስለምንጠቀም፣ ከሁሉም አቅጣጫ ጠቀሜታው የጎላ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ሲስተሙ ሌላ ክልል አለ ወይስ እዚሁ ዋናው ጽ/ቤት ብቻ ነው?
እዚህ  ዋናው ጽ/ቤት ነው ሲስተሙ ያለው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራው እዚሁ ነው፤ ነገር ግን አሁን አሰራሩ ኤሌክትሮኒክ ስለሆነ የትኛውም አመልካች የአዕምሮ ፈጠራውን፣ የንግድ ምልክቱንና ዲዛይኑን (ንድፉን) ካለበት ሆኖ በኤሌክትሮኒክ ሲስተም መላክና መመዝገብ እንዲሁም መከታተል ይቻላል፡፡
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በክልል ከፍቶ ለመንቀሳቀስ የታሰበ ነገር አለ?
በቅርቡ በክልሎች ቅርንጫፎችን ለመክፈት ሃሳብ አለን፡፡ አማራና ደቡብ ክልሎችን መርጠናል፡፡ ሌላው አካባቢም በሂደት ለመክፈት ሃሳብ አለ፡፡
ሁለቱ ክልሎች ቅድሚያ ያገኙበት ምክንያት ምንድን ነው?
ሁለቱን ከሌሎች በቅድሚያ የመረጥንበት ምክንያት የሚይዙትን የአካባቢ ስፋት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
ለምሳሌ አማራ ክልልን ብትወስጂ አብዛኛውን የሰሜኑን ክፍል፤ እነ ትግራይን፣ ከፊል ቤኒሻንጉልንና ከአፋርም የተወሰነውን ክፍል ይዞ  እንዲሰራ በማሰብ ነው፡፡ የደቡቡ ደግሞ የደቡብን አካባቢ አጠቃልሎ እስከ ድሬደዋ ወደ ምዕራብ ጭምር ተንቀሳቀሶ እንዲሰራ ታስቦ ነው፡፡ ለወደፊቱ ግን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹን ወደ አራት ከፍ ለማድረግና ስራችንን የበለጠ ለማቀላጠፍ እቅድ አለን፡፡
የቅጅ መብትን በተመለከተ ከዓለም አቀፍ የአዕምሮ ንብረት ድርጅት ጋር ልትሰሩ ያሰባችሁት ምንድን ነው?
ቅድም እንደገለፅኩት የቅጅ መብት አዋጅ በቅርቡ ፀድቋል፡፡ ይህ አዋጅ ባለ መብቶችን ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ እንግዲህ አዋጁን ተከትለን የቅጅ ባለመብቱን ጥቅም ለማስከበር በምን መልኩ ይሰራ የሚለውን የሲስተምና መሰል ድጋፎች ከዋይፖ ጠይቀናል፡፡
እነሱም ፕሮጀክቱን ፈቅደዋል፡፡ የሚሰሩት ስራዎች ወደፊት በሂደት በግልፅ  የሚታዩ ይሆናሉ፡፡ ዋናው ነገር እነሱ አሁንም በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ለመርዳት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው ነው፡፡

Saturday, 20 December 2014 12:47

ይድረስ ለህፃናት መምህራን

“ህፃናትን በፍቅር እናስተምራቸው”

     ልጆቼ የአምስትና የሶስት አመት ህፃናት ናቸው፡፡ የሚማሩት አንድ ትምህርት ቤት ሲሆን ትልቋ መካከለኛ የመዋዕለ ህፃናት፣ ትንሿ ደግሞ ጀማሪ የመዋዕለ ህፃናት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ከአንደበታቸው የማይጠፉ ሁለት አባሎች አሉ - “loser” እና “ shame on you” የሚሉ ናቸው፡፡ አንድ ቀን እኒህን አሉታዊ አባባሎች ከየት እንዳመጧቸው ስጠይቃቸው፣ ከትምህርት ቤት መሆኑን ነገሩኝ - ያውም ከመምህራኖቻቸው፡፡
ልጆቼ በሚማሩበት ት/ቤት መምህራን የህጻናቱን የዕለት ውሎ ለወላጆች ሪፖርት የሚያደርጉበትና ወላጆችም መመልከታቸውን ከአስተያየት ጋር (ካላቸው ማለት ነው) አክለው ፈርመው የሚልኩበት “ኮሙኒኬሽን ቡክ የሚሉት ትልቅ ጥራዝ አለ፡፡ በሌሎቹም የግል ት/ቤቶች ይኖራል ብዬ አምናለሁ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ በመጀመሪያዋ ልጄ የ “ኮሙኒኬሽን ቡክ” ላይ ዲሲፕሊን በሚለው ስር “ጥሩ” የሚል አስተያየት ሰፍሮ በማየቴ (ከወትሮው ዝቅ ያለ ነው) ምክንያቱን ጠየቅኋት፡፡
እሷም “ግድግዳ ላይ ስለፃፍኩ ነው…” አለችኝ
“ይቅርታ ጠየቅሽ?”
“አዎ፤ መጀመርያ የቅጣት ወንበር ላይ ተቀመጥኩና የክፍል ልጆች ጮክ ብለው “loser እና  shame on you” እንዲሉኝ ሚስ አዘዘቻቸው፡፡ ከዚያም ሚስን ይቅርታ ጠይቄ ወደ መቀመጫዬ ተመለስኩ” በማለት ሂደቱን አስረዳችኝ፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ነገር ሰምቼ ስለማላውቅ ደነገጥኩ፡፡ ሃሳብም ገባኝ፡፡ “አንቺም ሌሎችን እንደዛ ብለሽ ታውቂያለሽ?” ጠየቅኋት፤ ልጄን፡፡ “አዎ ብዙ ቀን እከሌ እና እከሌን ብለናቸዋል”፡፡ የልጄ መልስ ነበር፡፡ በከተማችን በሚገኙ አምስት የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪ የሆኑ ህፃናትን ጠይቄ ድርጊቱ በእነሱም ት/ቤቶች እንደሚፈፀም ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ልጆች በስነስርአት ታንፀው እንዲያድጉ ከተፈለገ፣ ያጠፉት ጥፋት ምን እንደሆነ በትክክል ተረድተው፣ ከጥፋታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ቅጣት ያልተገባ ባህርይን ወይም ድርጊትን ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ እንደሚያግዝ አያከራክርም፡፡ ሆኖም በተለይ በህፃንነት ዕድሜ ባሉ ተማሪዎች ላይ የሚፈፀመው ቅጣት ጥንቃቄ የተሞላበትና ያልተፈለገ ውጤት የማያመጣ መሆን ይገባዋል፡፡
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በልጆች ስነልቦና ላይ የሰሩትና በሙያቸው መምህር የሆኑት አቶ ማናዬ አደላ፤ ህፃናትን እንዴት ከጥፋት እንዲቆጠቡ ማድረግ እንደሚቻል ያስረዳሉ፤ “የመጀመሪያው አማራጭ የህፃናትን መልካም ስነምግባር ማበረታታት፣ ህፃናቱ ጥሩ ባህርይ እንዲላበሱ ያደርጋል፤ እግረመንገዱንም መጥፎውን እንዳይቀጥሉበት ይከለከላል፡፡ ነገር ግን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ከስነ ምግባር ውጭ የሆኑ ነገሮችን መልመዳቸው ስለማይቀር ተገቢ ማረሚያ መንገዶችን መጠቀም ይገባል፡፡ ከማረሚያ መንገዶቹ አንዱ ቅጣት የምንለው ነው፡፡” የሚሉት አቶ ማናዬ፤ በስነልቦና ሙያ ቅጣት ሁለት አይነት ነው፡- አዎንታዊና አሉታዊ ቅጣት” በማለት ያብራራሉ፡፡
“አሉታዊ ቅጣት በድርጊት (አካላዊ ቅጣት ማለት ነው) ወይም በቃላት የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ ይህ አይነቱ ቅጣት አካላዊ ጉዳትና ስነልቦናዊ ተፅዕኖ ስላለው በፍፁም አይመከርም፡፡ አዎንታዊ ቅጣት የሚባለው ምንም አይነት ስነልቦናዊና አካላዊ ጉዳት በህፃናቱ ላይ ሳያደርሱ፣ ከመሰረታዊ ፍላጎቶች ውጪ የሆኑ ነገሮችን እንደ መቀጣጫ በማስቀረት ስህተታቸውን  ደግመው እንዳይፈፅሙ ማስተማር አይነት ዘዴዎችን ያካተተ ነው፡፡” ይላሉ - ባለሙያው፡፡   
በህፃናት ላይ የሚሰነዘር ስድብና ማላገጥ የህፃናቱን በራስ የመተማመን መንፈስ ይጎዳል፣ ከሌሎች ጋር ሊኖራቸው የሚገባ መቀራረብን ያሳጣል፣ ለትምህርት ያላቸውን ተነሳሽነት ይገድለዋል፣ ፍርሀት በውስጣቸው  እንዲፈጠር በማድረግ የፈጠ አቅማቸውን ያዳክማል ያጠፋል ፣ ሌሎች ነገሮችን እንዳይሞክሩ ያደርጋል፣ የበታችነት ስሜት ይፈጥራል፡፡ ከዚያም አልፎ ትምህርት ቤትን እንዲጠሉና አንሄድም እንዲሉ ያደርጋል፣ የቀጣውን አስተማሪ ከእነሚያስተምረው ትምህርት ጭምር እንዲጠሉ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
ህፃናት መቀጣት ያለባቸው በመምህራቸው ብቻ እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያው፤ ተማሪን እያስጨበጨቡ  በቅጣት ላይ ማሳተፍ በተለይ በአቻ እድሜ ላይ ሲሆን የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ እጅግ ከባድ ነው ባይ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ እድሜ ላይ ያሉ ልጆች  በመምህራቸው ትዕዛዝ የክፍላቸውን ተማሪ  “loser” እና  “shame on you” የመሳሰሉ አባባሎችን በመጠቀም እንዲያሾፉበት ሲደረግ ተማሪው ላይ የበታችነት ስሜት ይፈጠራል፤ ይህ ደግሞ በህፃናት ላይ መፈፀም ከሌለባቸው ድርጊቶች አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም የበታችነት ስሜት የሚሰማው ህፃን ተወዳዳሪነቱ ይቀንሳል፣ በራስ የመተማመን ስሜት ያጣል፣ በአጠቃላይም እጅግ አፍራሽ ውጤት የሚያስከትል ድርጊት ነው ይላሉ፤ አቶ ማናዬ፡፡ከሁለት አመት እስከ ሰባት አመትና ከሰባት እስከ አስራ አንድ አመት ያሉት ጊዜያት እጅግ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው፣ በህፃናት እድገት ላይ ወሳኝ ጊዜያት ናቸው ያሉት ባለሙያው፤ በዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂ እጅግ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል የሚባሉ የእድሜ ደረጃዎች መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡ ይህ እድሜ የልጆችን ሁለንተናዊ እድገት ማበረታቻ እንጂ ማጨናገፊያ መሆን የለበትም፡፡ አስተማሪዎች እጅግ ብልጠት የታከለበት ቅጣትን በመጠቀም ተገቢ ያልሆኑ ባህርያትን ማረም እንዳለባቸውም ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡
 የልጆቼ ትምህርት ቤት ሄጄ ዳይሬክተሯን አነጋግሬ ነበር፡፡ “ልጆች እንዴት ከትምህርት ቤት ስድብ ተምረው ይመጣሉ፤ ስድቦቹ ለመዋዕለ ህፃናት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለአዋቂም እንኳን እጅግ የሚያሸማቅቁ ናቸው፣ እንዲህ አይነት አባባሎች በትምህርት ቤቱ እንዳይበረታቱ ሊደረግ ይገባል” በሚል ያቀረብኩትን ሃሳብ በቀናነት ተቀብለውኛል፡፡ ለመምህራኑ ተከታታይ ስልጠናዎችን ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሆኑም ዳይሬክተሯ ጠቁመውኛል፡፡ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም እንዲህ ያለ የህፃናትን በራስ የመተማመን ስሜት የሚጐዳ ስድብና ድርጊት ከመፈፀም በመታቀብ፣ ያጠፉ ህፃናትን አስተማሪ በሆነና ሰብዕናቸውን በማይጐዳ መልኩ መቅጣት ይኖርባቸዋል፡፡
በለጋ እድሜ ላይ ያሉ ህፃናትን መስደብና ማሾፊያ ማድረግ በትምህርታቸውና በማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል መገንዘብ ይገባል፡፡  ህፃናትን በፍቅር እናስተምራቸው!!

Published in ባህል
Saturday, 20 December 2014 12:38

የሴት ኮንዶም

     ኤች አይቪ ኤድስን ጨምሮ ሌሎች ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳቢያ የሚተላለፉ በሽታዎችና ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችል የሴት ኮንዶም በዲኬቲ ኢትዮጵያ ወደ አገራችን አስመጥቶ ለገበያ ከቀረበ ቆየት ብሏል፡፡ ኮንዶሙን ሁልጊዜና በአግባቡ ከተጠቀሙበት በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችንም ሆነ ያልተፈለገ እርግዝናን የመካላከል አቅሙ አስተማማኝ እንደሆነም የጤና ባለሙያዎችን ይናገራሉ፡፡ ዲኬቲ ኢትዮጵያ ኮንዶሙን በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች እንዲጠቀሙበት በማድረግ አበረታች ውጤት አስገኝቷል ሲባል ሰማሁና ጉዳዩን ከራሳቸው ከተጠቃሚዎቹ አንደበት ለመስማት ወደ ስፍራው ተጓዝኩ፡፡
በአዲሱ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ሳቢያ ምስቅልቅሉ ከወጣው የመርካቶው ሰባተኛ መንደር የደረስኩት ባለፈው ማክሰኞ አመሻሹ ላይ ነበር፡፡ ስፍራው በወሲብ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች በስፋት የሚገኙበት በመሆኑ በቂ መረጃዎችን እንደማገኝ እምነት ነበረኝ፡፡ ከአዲስ ከተማ የመሰናዶ ት/ቤት ፊት ለፊት የሚገኙት ቅያሶች በሙሉ ወደ እነዚሁ አካባቢዎች የሚያደርሱ በመሆናቸው አንዱን መንገድ ይዤ ቁልቁል ወረድኩ፡፡
በቆርቆሮና በጣውላ እርስ በርስ ተዛዝለው የተሰሩና በሮቻቸው አጫጭር የሆኑትን የሴተኛ አዳሪዎቹን ቤቶች እያለፍኩ ወደመሀል ዘለቅሁ፡፡ የቀድሞው ቀበሌ 12 በርካታ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች የሚገኙበት አካባቢ ነው፡፡
ሴቶቹ ከተለያዩ የአገራችን ክልሎች የመጡ መሆናቸውንና በወሲብ ንግድ ለዓመታት ተሰማርተው እንደቆዩ ነገሩኝ፡፡ ስለኤችአይቪ/ ኤድስና ጥንቃቄ በጎደለው ወሲብ ሳቢያ ስለሚከሰቱ በሽታዎች በቂ ግንዛቤም አላቸው፡፡ ኮንዶምን ሁልግዜ የመጠቀም ፍላጎት ቢኖራቸውም አብዛኛውን ጊዜ ያለኮንዶም ወሲብ ለመፈጸም የሚፈልጉ አንዳንድ ግድየለሽ ደንበኞቻቸው ያለፍላጐታቸው ከኮንዶም ውጭ ወሲብ እንዲፈፅሙ እንደሚይስገድዷቸው አጫወቱኝ፡፡ “ብዙውን ጊዜ በኃይል እየተጠቀሙ ያለኮንዶም ወሲብ ለመፈጸም የሚፈልጉ ወንዶችን ጮኸን እናስይዛቸዋል፡፡ እርስ በርሳችን በመረዳዳት ሴቲቱን አስገድዶ ያለኮንዶም ሊገናኝ የሚፈልገውን ወንድ በፖሊስ እናሲዛለን፡፡ አንዳንዴ ግን ወንዶች ያለኮንዶም ወሲብ ለመፈፀም የሚያቀርቡልን ማባበያ እያታለለን እኛም በፍቃደኝነት እንፈፅማለን፡፡ አንዳንዱ ወንድ ደግሞ ተስማምተን በኮንዶም ወሲብ ማድረግ ከጀመርን በኋላ ያጠለቀውን ኮንዶም አውልቆ በመጣል ያለኮንዶም ይገናኛል፡፡ ምን ታደርጊዋለሽ፡፡ ህይወት እንዲህ ናት!”
ሴቶቹ ህይወታቸው ስቃይና ሐዘን የተሞላበት እንደሆነና ራሳቸውን እንደ ሰዉ ቆጥረው ተስፋ ለማድረግ እንደማይችሉ ነገሩኝ፡፡ በቅር/ጀ ወደ አገራችን መጥቶ ገበያ ላይ ስለወሰው የሴቶች ኮንዶም ያውቁ እንደሆነ ጠየቅኋቸው፡፡ ሁሉም ሴቶች ስለ ኮንዶሙ ያውቃሉ፡፡ ሞክረውታልም፡፡ እንዴት ነው ታዲያ ስል ጥያቄዬን ቀጠልኩ፡፡
“በወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተሽ በራስሽ ፍላጎትና አማራጭ መጓዝ አትችይም፡፡ ደንበኛሽ ገንዘቡን እስከከፈለ ድረስ እሱ በሚፈልገው መንገድ ማስተናገድ አለብሽ፡፡ ይህንን ስታደርጊ ታዲያ ራስሽን ለበሽታና ለሞት አጋልጠሸ አይደለም፡፡ የሴት ኮንዶም በመምጣቱ ሁላችንም ደስተኞች ነን፤ ምክንያቱም በእኛ ስራ ኮንዶም መጠቀም የደንበኛሽን በጎ ፍቃደኝነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ ወንዱ በወሲብ ላይ እያለን ኮንዶሙን በማውለቅ ያለኮንዶም ሊገናኘን ስለሚችል ይህ ኮንዶም ከእነዚህ ችግሮች ይታደገናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በስካር ኃይል ያለኮንዶም ሊያወጡን ከሚፈልጉ ወንዶች ይጠብቀናል፡፡ አንዳንድ ወንዶች ገንዘባቸውን ከፍለው ለወሲብ ዝግጁ መሆን ሲያቅታቸው ኮንዶሙን አውልቀው ያለ ኮንዶም ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ወቅት የሴት ኮንዶሙን አጥልቀን ዝግጁ ከሆንን ያለ ችግር እናስተናግዳቸዋለን፡፡ ኮንዶሙ እነዚህ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ሁሉ ጉዳቶችም አሉት፡፡ የሴት ኮንዶሙ ለስምንት ሰዓታት በማህፀን ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል ብለው ነገረውናል፡፡ ስለዚህ ኮንዶሙን ቀደም ብለን አጥልቀን ደንበኞቻችንን እንጠብቃለን፡፡ ደንበኞቻችን በአብዛኛው ደስተኞች አይደሉም፤ አንዳንዶቹ አስተማማኝ አይደለም በማለት ኮንዶም አጥልቀው ይገናኙናል፤ በዚህ ጊዜ ህመም ይሰማናል፡፡ ድርቀት ስለሚፈጠርም ምቾት ያለው ወሲብ አንፈፅምም፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ በሰውነታችን ውስጥ ሲቀመጥና በተለይ ብዙ ስንቆም ምቾት ይነሳናል፡፡ ብዙውን ጊዜ የሴት ኮንዶሞችን የምንጠቀመው በበዓላት ዋዜማና ግርግር በሚበዛባቸው ጊዜያት ነው፡፡” ከሴቶቹ ጋር ስለሴት ኮንዶም ያደረግሁትን ቆይታ ካጠናቀቅሁ በኋላ ስለ ሴት ኮንዶም ምንነት ጠቀሜታና የጎንዮሽ ጉዳት እንዲያብራሩልኝ የማህፀን ፅንስ ስፔሻሊስት ዶክተር የኔነህ ታምራትን አነጋገርኳቸው፡፡
የሴቶች ኮንዶም በተለያዩ የዓለማችን አገራት በስፋት በጥቅም ላይ የሚውሉ ቢሆንም በአገራችን እምብዛም የማይታወቅና ከጥቂት ጊዜያት በፊት እንደገባ የገለፁልኝ ዶክተሩ፤ ህብረተሰቡ ስለሴት ኮንዶም ምንነትና አጠቃቀም እምብዛም ባለማወቁ በአግባቡ ጥቅም ላይ አልዋለም ብለዋል፡፡
የሴት ኮንዶሞች በተለያዩ አይነትና ብራንድ በዓለም ገበያ ላይ የሚገኙ ሲሆን  Femidom, Fc femeal condom, Reality, Dominiquie femy, Protectiv care, 7C2, 7C የተባሉት ይገኙበታል፡፡ በአገራችን ገበያ ላይ የሚገኙት 7C2 የተባሉት ኮንዶሞች ናቸው፡፡ የሴት  ኮንዶም ላቴክስ ከሚባልና ከጎማ ተክል ከሚመነጭ ፈሻሽ የሚሰራ ሲሆን በአግባቡና ሁልጊዜ ከተጠቀሙበት ያልተፈለገ እርግዝናንም ሆነ ኤችአይቪ/ ኤድስን ጨምሮ ሌሎች በግብረስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ያስችላሉ፡፡የሴት ኮንዶሞች በመጀመሪያ አካባቢ ለአጠቃቀም  ምቹ አለመሆን፣ ምቾት አለመሰማት አይነት ችግሮች እንዳሏቸው ባይካድም ሲለመዱ ግን ይህ አይነቱ ስሜት እንደሚጠፋም ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡ የሴት ኮንዶም ከተጠቀመች ሴት ጋር ወሲብ ለመፈፀም የሚዘጋጅ ወንድ ኮንዶም ማድረግ ይጠበቅበታል ወይ ለሚለው ጥያቄም ዶክተሩ ሲመልሲ ይህ እጅግ አደገኛና ሁለቱንም የወሲብ ተጓዳኞች ችግር ላይ የሚጥል ነገር ነው፤ ሴቷ ኮንዶሙን ከተጠቀመች ወንዱ መጠቀም አይኖርበትም፡፡ ሁለቱም ከተጠቀሙ ግን ድርቀት በመፍጠር ኮንዶሙ የመቀደድና የመላጥ ችግር ያስከትላል፤ ይህም በሽታ በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው እንዲተላለፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡



Published in ዋናው ጤና
Page 5 of 13