በሁለት ትውልዶች የፍቅር፣ የባህልና የወግ ሁኔታ ላይ የሚያጠነጥነው “ውቤ ከረሜላ” ልብወለድ መፅሃፍ (ቁጥር አንድ) ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ በደራሲ ኤልያስ ማሞ የተፃፈው ልቦለድ፤ በዋናነት በኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመን የነበሩ የፍቅር፣ የጋብቻ፣ የወግና የባህል ሁነቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን በልማት ምክንያት እየተቀየሩና እየጠፉ ስላሉ እንደነ ውቤ በረሃ ያሉ አካባቢዎችንም ይዳስሳል ተብሏል፡፡ ልብወለዱ ለደራሲው ሁለተኛው ስራው ሲሆን ከዚህ ቀደም “እንጦሽ” በተሰኘ የአጫጭር ልብወለዶች ስብስብ ውስጥ ሥራው ተካትቶለታል፡፡ “ውቤ ከረሜላ ቁጥር 2” በመጪው ሰኔ፣ ቁጥር 3 ደግሞ የዛሬ ዓመት ገደማ ለአንባቢ እንደሚደርስም ደራሲው ገልጿል፡፡ የአሁኑ ልብወለድ በ244 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ለአገር ውስጥ በ50 ብርና ለውጭ አገር በ19 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

   በአማኑኤል ግርማ የተሰናዳውና የናይጄሪያዊውን ቀልደኛ የአክፓስ ቀልዶች የያዘው “የአክፓስ ቀልዶችና ምፀቶች” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ለገበያ ቀረበ፡፡ የቀልደኛውን 100 ያህል ቀልዶች ለአንባቢ በሚስማማ መልክ በመተርጐም ለአንባቢ ያደረሰው አማኑኤል ግርማ፤ በመፅሀፉ ላይ የተገለፀው ገፀ-ባህሪ ራሱ ቀልደኛው አክፓስ እንደሆነ በመግቢያው ላይ ጠቁሟል፡፡ በ113 ገፆች የተሰናዳው መፅሀፉ፤ በ30 ብር ከ35 ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡

    በፖርቹጋል ኤምባሲ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀ የፖርቹጋልንና የኢትዮጵያን የ500 ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚዘክር ኪነ ጥበባዊ ፕሮግራም በብሄራዊ ቴአትር ቀረበ፡፡ ባለፈው ሰኞ ከ6ሰዓት ተኩል ጀምሮ በተካሄደው በዚህ ዝግጅት ላይ በፖርቹጋልና በኢትዮጵያ አርቲስቶች የተለያዩ የጥበብ ስራዎች የቀረቡ ሲሆን የሁለቱም አገራት ተወካዮች ታድመውበታል፡፡ እውቁ ኢትዮጵያዊ የፒያኖ ተጫዋች ግርማ ይፍራሸዋና ፓርቹጋላዊቷ የፒያኖ ባለሙያ ቬራ ኢስትቬዝም የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለታዳሚዎች አቅርበዋል፡፡ በዮሃንስ ተፈራ፣ በእስራኤል መሃሪና በዝናው ደሳለኝ ተፅፎ በተስፋዬ እሸቱ የተዘጋጀው “እንቁ” የተሰኘ ሙዚቃዊ ድራማ ቀርቦ ታዳሚውን ያዝናና ሲሆን የመርድ ታደሰ፣ የቴዎድሮስ ሀጎስ፣ የደረጄ ደምሴና የታምራት ገዛኸኝ የስዕል ስራዎችም ለእይታ ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር በትላንትናው እለት ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ በሩሲያ የሳይንስና የባህል አዳራሽ “ሰላም ለሴቶች ከጓዳ እስከ አደባባይ” በሚል መርህ የኪነ ጥበብ ዝግጅት አካሂዷል፡፡ ፕሮግራሙ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀንን አስመልክቶ የተዘጋጀ ሲሆን ወንድና ሴት ደራሲያን ጥቃት ላይ ያተኮሩ ስራዎቻቸውን ለታዳሚዎች አቅርበዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ በቅርቡ በአምስት ወንዶች የመደፈር ጥቃት ደርሶባት ህይወቷ ያለፈው ታዳጊ ሃና ላላንጎ የታወሰች ሲሆን የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓትም ተካሂዶላታል፡፡
ማህበሩ በየወሩ “ጥበብ እንቃመስ” የተሰኘ የኪነ ጥበብ ዝግጅት የሚያካሂድ ሲሆነ የአሁኑን ፕሮግራም ለየት የሚያደርገው በሴቶች ጥቃት ላይ ትኩረት በማድረጉና በየዓመቱ የሚካሄደውን የ16 ቀን የፀረ ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ ለማሰብ የተዘጋጀ በመሆኑ ነው ብለዋል - የማህበሩ ፕሬዚዳንት ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለ፡፡ በእለቱ ሴት ተማሪዎች የሚደርሱባቸውን ፆታዊ ጥቃትና ትንኮሳ እንዴት ቴኳንዶ በመማር መከላከል እንደሚችሉ ግንዛቤ የሚሰጥ የቴኳንዶ ትርኢትም ቀርቧል፡፡

       በጋዜጠኛ ሰለሞን ታደሰ የተጻፈው “የሸገር ወጎች ቁጥር ሁለት” መፅሀፍ ለንባብ በቃ፡፡ የተለያዩ ወጎችና እውነተኛ ታሪኮች የተካተቱበት መፅሀፉ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ዱባይ ስለ ተዘረጋ ሚስጥራዊ ቡድን፣ ስለ ነጋዴዎቹ ሴተኛ አዳሪዎች፣ በወሲብ ፊልም ላይ ስለተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችና ሌሎች እውነተኛ ታሪኮች ላይ ያተኮረ ሲሆን መፅሀፉ ለደራሲው ሶስተኛ ስራው መሆኑ ታውቋል፡፡ በ183 ገፆች የተቀነበበውና በ50 ብር ከ90 ሳንቲም ለገበያ የቀረበው መፅሀፉ፤ በጃፋር መፅሀፍ መደብር አከፋፋይነት እየተሰራጨ ሲሆን በሁሉም የመፃህፍት መደብሮች እንደሚገኝ ደራሲው ገልጿል፡፡ ጋዜጠኛው ከዚህ ቀደም “ቦሌ ፒኮክ ጋር ጠብቂኝ” እና “የሸገር ወጎች ቁጥር 1” የተሰኙ መፃህፍትን ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

ጋለሪያ ቶሞካ ነገ ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ በአርቲስት ዘላለም ግዛው የስዕል ስራዎች ላይ ውይይት ያካሂዳል፡፡ ጋለሪው ከአንድ ወር በፊት “ግልፅና ስውር፡ ከብርድልብስ ስር” የተሰኘ የሰዓሊውን ስራዎች የሚያስቃኝ አውደ ርዕይ ለእይታ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በነገው ውይይት ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የስዕል አድናቂዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ጋዜጠኞች እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡ ውይይቱ በሰዓሊው ስራዎች፣ በስዕል ፍልስፍናውና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን ሰዓሊዎችና የስዕል አድናቂዎች እንዲታደሙ ጋለሪ ቶሞካ ግብዣ አቅርቧል፡፡

Saturday, 13 December 2014 11:14

ራሄል ጉዲት

      የሰው ልጅ ዛሬ ከደረሰበት ወይም ከቆመበት ቦታ ታሪኩ አይጀምርም፡፡ ወደ ኋላ የሚተረተር፣ የሚጎለጎል ቱባ መምጫና መገለጫ አለው፡፡
እነሆ ታሪክ …
አባቴ እናቴን አገባት፡፡ ክብር ዘበኛውና የቤት እመቤቷ ተጋብተው ሲወልዱ - ሲወልዱ - ሲወልዱ - ሲወልዱ - ሲወልዱ … አስራ ስድስተኛ ልጃቸውን እኔን ወለዱ፡፡ ለኔ መወለድ - እናቴ እንቁላሏንና ማህፀኗን ስታዋጣ፣ አባቴ ደግሞ የዘር ፍሬውን አበረከተ፡፡ ከተወለድኩ በኋላም እናቴ ጡቷንና ጀርባዋን ስትቸረኝ - አባቴ ገንዘቡን፡፡ እናቴ - አባቴን አራት ለሁለት ስለምትመራው ነው መሰለኝ -- ለሷ ያለኝ ፍቅር እንደ ምድር ያለ ካስማ፣ እንደ ሰማይ ያለ ባላ የፀና ነው፡፡
ዛሬ አድጌያለሁ …
ያደገ ሰው አባወራ ለመሆን እቤቱ ውስጥ እማወራ ያሳድራል፡፡ እቤቴ የምታድር እማወራ የለችኝም - የምትመላለስ ግን አለችኝ፡፡ ራሄል ስሟ ነው፡፡ ራሄል ቆንጆ ነች፡፡ ራሄል ሁሌም ሌላ ራሄል ነች፡፡ ራሄል ሁሌም ግራ ታጋባኛለች፡፡ በማይለወጥ ቆንጆ መልኳ፣ እንደ እስስት በየሰከንዱ አዳዲስ ሰብዕና  እየተላበሰች፣ ይኼው ግራ ስታጋባኝ አምስት ዓመት ሞላኝ፡፡ ፍቅር ማለት እሷን ለማወቅ የማደርገው ጥረትና በየዕለቱ የምገባው እልህ እስኪመስለኝ ድረስ፡፡
የዛሬ ፊቷን ለጣረ ሞት አምስት ጉዳይ ሲቀረው ነው ይዛው የመጣችው፡፡ እንዲህ ሆና ደግሞ አይቻት አላውቅም፡፡ ደግሞ ዛሬ ምን ገጥሟት ይሆን? ምላሷ ሳይበጠር፣ እንደተንጨፈረረ አፏ ዋሻ ውስጥ ተቀምጧል፡፡ እንደፈራሁት ሳታበጥረው ወሬ ጀመረችበት፡፡
“ካንሰር ይዞኛል!”
“ምን!?”  አልኩ፡፡ ሳልሰማት ቀርቼ አይደለም፡፡ እንኳንስ ድምጿ የሆዷ ጉርምርምታ ሳይቀር በሚሰማኝ ርቀት ላይ ነው ያለሁት፡፡ ግን ያለችው ምንም አልገባኝም፡፡
“አይገባህም!? የጡት ካንሰር ይዞኛል፡፡ እንዴት ይሄ በሽታ ለኔ ይሆናል?  እኔ እኮ ዮዲት ጉዲት ሳልሆን ውቧ ራሄል ነኝ፡፡ ለተቆረጠ ጡቴ መበቀያ - የማቃጥለው ቤተ መቅደስና የማሳድደው ካህን የለኝም…” ወይ ራሄል ጉዲት! ዛሬ ደግሞ እንዴት ያለ ወሬ ነው ይዛብኝ የመጣችው!? አንገትም ሆነ  ጅራት የለውም እኮ፡፡ ምንድነው የምላት? ለሚቆረጥ ጡት የሚሆን ማፅናኛ እንዴት ያለ ነው … ልግጠም ይሆን?
ልጅ እያለሁ፣ አልቅሼ እናቴ ስታፅናናኝ ወይም ተነጫንጬ ስታስተኛኝ፣ በዜማና በግጥም ነበር፡፡ ሞልቶ የገነፈለ የፍቅር እመቤት ስለነበረች፣ ዜማና ግጥም ለማፍለቅ የምናብ ዳረጎት ወይም ብድር አያስፈልጋትም፡፡
ለዚህም ይመስለኛል ለግጥም ቅርብ የነበርት፡፡ ይሄንን ቅርበቴን  ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘብኩት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነበር፡፡
እንደ አማርኛ የፊደል ገበታ  - በቀላሉ የማይለመድ ፊት ነበራቸው፡፡ ሀ - ላይ ፈግገው፣ ሁ - ላይ ይዳምናሉ - የአምስተኛ ክፍል የአማርኛ መምህራችን፡፡ እንደ ዛሬ - ለበነጋው ሰርተነው የምንመጣው የቤት ስራ አዘዙን፡፡ የቤት ስራው ግጥም ነበር፤ ግጥሙ ደግሞ ስለ ወፍ የሚተርክ መሆን አለበት አሉን፡፡
በበነጋው ስለ ወፍ የሚተርከውን ግጥም ፅፌ የተገኘሁት ተማሪ እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ምድረ የአምስተኛ ክፍል ውሪ ሁላ …ስለ ትረካ ምንነት የት ታውቅና - እንኳን ስለ ወፍ መተረክ ቀርቶ፡፡
አማርኛ መምህራችን እኔን አመስግነው… አሞጋግሰው …ሌላውን በጉማሬ (በእንስሳው ሳይሆን ባለንጋው) ሶስት ሶስቴ ቂጥ ቂጡን ገሽልጠው ሲያበቁ …ስለ ወፍ የሚተርከውን ግጥሜን ወጥቼ እንዳነብ ጋበዙኝ፡፡
ወጥቼ አነበብኩ…
በጠፍጣፋ ድንጋይ ከተዘጋ በሩ
እናት አትገኝም እንደ ወፍ ቢበሩ፡፡
አንብቤ ሳበቃ የጓደኞቼ ጭብጨባና የመምህሬ ሁለት ኩርኩም ተበረከተልኝ፡፡
ዛሬ አድጌያለሁ ብያለሁ … ያደገ ሰው ነኝ፡፡ ያደጉ ሰዎች አንብበው የሚረዱት፣ የሚወዱትና እኔንም የሚያደንቁበት ግጥም እፅፋለሁ፡፡ ያደጉ ሰዎች በስመጥር ገጣሚነቴ ነው የሚያውቁኝ፡፡ ቤቴ የምትመላለስ እማወራዬ ደግሞ ስለ መሞት እያወራችኝ ነው፡፡ ስለ ህመሟ ግጥም መፃፍ እንጂ ከህመሟ ልፈውሳት እንደማልችል እያስገነዘበችኝ ያለች ትመስላለች፡፡
አውቃለሁ - መፈወስ ፈጠራ ይጠይቃል፡፡ ፈጠራ ከምንም ነገር ውስጥ የሆነ ነገርን ማስገኘት ነው፡፡ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው ነገር ግን ፈጠራ አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እግዜሩስ  ቢሆን አዳምን ብቻ አይደለም እንዴ የፈጠረው፡፡ ከአዳም ወዲህ - ከሔዋን ጀምሮ ሰው ፈበረከ እንጂ አልፈጠረም እኮ!? እኔም ገጣሚው - ግጥም የፈጠርኩት ያኔ ነው፡፡ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ - ይኸው እስከ ዛሬ የግጥም መፈብረኪያ ማሽን ሆኜአለሁ፡፡
ራሄል ጉዲት - ባልተበጠረ ምላሷ ማውራቷን ቀጥላለች…
“…ሞቴ በእቅዴ ኩሬ ውስጥ ረግቶ የሚኖር ታዛዤ ነው … ሞቴ እንደ ደራሽ ውሃ ድንገት ከተፍ ባይ አይደለም፡፡ እንድታውቀው የምፈልገው ነገር ግን ጡቴን አስቆርጬ፣ ወንድ ደረት ሆኜ መኖር እንደማልፈልግ ነው…”
ኧረ ቆይ - ጡት ምንድነው!? እስከ ዛሬ ስለ ጡት ምንም አይነት የተለየ ነገር አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ የምር ግን የራሄል ጡት፣ ከጡት የዘለለ ምንነት አለው እንዴ?
አዎ! አለው፡፡
እና ጡት ምንድነው?
ጡትስ ራሄል ነው… ጡትስ ራሄል ነው፡፡
ራሄል እያወራች - እኔ እንዲህ በሀሳብ እዳክራለሁ!!
“…አይዞሽ ራሄል - ይሄ በሽታ ባንቺ ላይ ብቻ የሚደርስ በሽታ አይደለም፡፡ ማለቴ…”
“ባንተ ላይ ይደርሳል!?” አለችኝ  አቋርጣኝ፡፡
“ማለቴ… ያው በሌሎች ሴት እህቶቻችንም ላይ የሚደርስ ነው ብዬ ነው…”
“እኔ ሌሎች ሴት እህቶቻችሁን አይደለሁማ - እኔ ራሄል ነኝ” አለችኝ፡፡    
“ይገባኛል! ይገባኛል ራሄል -- ግን በደንብ አስቢው እስቲ… ለአንድ ጡት ይሄን ያህል መሆን የለብሽም … ደግሞስ - ዘንድሮ ምን ጡት አለና ነው እንዲህ መጨነቅ መጠበብሽ --- የዘንድሮ ሴቶች ከወንዶች የሚለዩት እኮ ደረታቸው ላይ ባለች ብጉንጅ የምታክል አጎጣጉጤያቸው እኮ ነው … እናም…”
አሁንም ሳታስጨርሰኝ “ጡትን እንዴት አባህ ነው ያየኸው አንተ!? ለደነዝነትህ ልክ አጥተህለት አልተገለጠልህም እንጂ ሴት ልጅ እኮ ጡቷን ነች፡፡ ጡት ማለት - ለሴት ልጅ ባሏን ማሰሪያ ገመዷ -- ከስሯ እንዳይወጣ ማድረጊያዋ… የማያልቅ የስኳር፣ የመጣፈጥ ተራራዋ ነው፡፡ በልጆቿ ልቦና ውስጥ ደግሞ እናት አማልክት ሆና የምትኖርበት ነው፡፡ ይገባሃል!? እድሜ ልካቸውን - ማን እንደ እናት - እያሉ እንዲኖሩ ማድረጊያ ምትሃቷ ጡቷ ነው…”
“እምልሽ - ጡት ካሉሽ በርካታ ሴትነትሽን ከሚገልፁ አካሎችሽ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እሱ ቢጎድልም…”
ራሄል ወሬዬን ልታስጨርሰኝ አትችልም
“ባይኖረኝም መኖር እችላለሁ አይደል!? እንዲህ ልትለኝ ነው ያሰብከው? አንተ ደደብ! ደደብ መሆንህን ስታቆም እመጣለሁ” ብላኝ ነበር የምትወጣው - ከላይ ያሰብኩትን ባወራት፡፡ ደግነቱ - የሰው መታደሉ አእምሮው ምላስ አልባ መሆኑም ላይ አይደል፡፡
አንዳንድ እውነት ደግሞ - እውነት ነኝ የሚለው -- እንደ ፈሪ ጀግና መሆን አይነት -- ወቅትና ክስተት ጠብቆ ነው፡፡ እስቲ አሁን ማ ይሙት፣ እኔስ ሆንኩ ራሄል  ከዛሬ በፊት ስለ ጡት እንዲህ አይነት አመለካከት ኖሮን ያውቃል? ጡትስ - ይኼን ያህል የመግዘፍ አቅም እንዳለው ገምተን እናውቃለን? በካንሰር አስታክኮ - ጡት ብቻ ሳልሆን - ሙሉ ራስሽን - ሙሉ አንቺን ነኝ ብሏት እርፍ አለዋ፡፡
እና እኔ ምን አባቴ ላድርጋት!?  ራሄል ጉዲት ከክፉ ቀን ከብዳ እያስጨነቀችኝ ነው፡፡ በህይወቴ የምጠላው ነገር ቢኖር ደግሞ ጭንቀትን ነው፡፡ በእስከዛሬው ሕይወቴ - እንግዲህ የዛሬውንም ጭምር ደምሬ መሆኑ ነው - የማልረሳቸው ሁለት ጭንቀቶች ውስጥ ዳክሬያለሁ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሁለቱም በሴት ሳቢያ የመጡ መሆናቸው ነው፡፡
የመጀመሪያው ጭንቄ የተወለደው፣ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነበር፡፡ ልክ እንደ ራሄል - ቆንጆና ግራ የነበረችዋን ሰብለን አፍቅሬ፡፡ ቤተሰቦቼ ከአስራ አምስት ልጅ ተርፏቸው - ለኔ ለብቻዬ የሚሰጡኝ የተለየ ፍቅር አልነበራቸውም፡፡ እናም በየደረስኩበት እፈልገዋለሁ፡፡ የተለየ ፍቅር የሚሰጠኝን ሰው በታላቅ ሀሰሳ ነበር የማፈላልገው፡፡ ያገኘሁ ሲመስለኝ ሁሉ ነገሬ ወከክ ብሎ ይከፈታል … እናም አፍቃሪ ነበርኩ፡፡
ልጅት ማፍቀሬን አውቃለች፡፡ አጠገቧ ስደርስ - የተቆጣች ቆቅ ትሆናለች፡፡ እንኳን ተቆጥታ ቆቅ እኮ ቆቅ ነች፡፡ የፊቴን ግርታ ስትመለከትና ስትንጨፈረር፤ ልቤ ውስጥ የሆነ … ነፍሴ የምትባለው እረቂቅ ሕዋሴ ውስጥ -- ግዙፍ ያመድ ተራራ ያለ ነበር የሚመስለኝ …መላ አካሌ እንደ አሞሌ ነጥቶ ፊቷ የቆምኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ መሸበሬ ይገባታል --- ጅምር ቆቅነቷ መርበድበዴን ሹክ ብሏታል … ከቆንጆ  ለጋ አይኗ ውስጥ እንደ ጅራፍ - አወፍራ በገመደችው የቁጣ መብረቋ -- መንፈሴን ነበር የምትለጠልጠው፡፡ ያ - የመንፈስ ግርፋቴ ያወጣው ሰንበር፣ ዛሬም ድረስ የጠፋ አይመስለኝም፡፡ አሃ! ባይጠፋ ነው እንጂ …እንደውም በራሄል የጡት አስኮርባጅ - የካንሰር ጉማሬ አዲስ ጓደኛም ተጨመረለት፡፡
ጨንቆኝ ነበር፡፡ ጠብቦኝ ነበር፡፡ የምሆነው የምሰራው ጠፍቶኝ ነበር፡፡ በኋላ ላይ በአንድ ጓደኛዬ አይዞህ ባይነት -- መንደራችን ውስጥ ደብዳቤ በመፃፍ ለሚታወቅ  ልጅ - ስፈራ ስቸር ሄጄ ፍቅር እንደያዘኝ ነገርኩት፡፡ ስለ ፍቅሬ ደረጃም ሆነ ስለ ልጅቷ ማንነት መጠየቅ ሳያስፈልገው ደብዳቤውን ፃፈልኝ፡፡
“ሙሴ የያዘው በትር እባብ ሆነ -- የባቢሎን ግንብ ፈራረሰ -- የግብፅ ከተሞች በፒራሚድ አጌጡ -- የዳዊት ወንጭፍ ግዙፉን ጎልያድ ጣለች --- አንዳንዴ - በሕይወት ውስጥ የማይሆን የሚመስለን ነገር ሁሉ ይሆናል፡፡ የኔም አንቺን ማፍቀር እንደዚያው ነው እንዳያልቅ - እንዳይደረስበት ሆኖ የተዘረጋው፡፡ ሰፊ ሰማይ - አገርሽ ነው፡፡ ሰማዩ እንብርት ላይ ብቻዋን እንደረጋች ኩንስንስ ሴት ወይዘሮ --- በክብነቷ ተኩራርታ የተቀመጠችው ጨረቃ አንቺ ነሽ፡፡ ከዋክብት ለክብርሽ ጠብ እርግፍ የሚሉ ደንገጡሮችሽ…” ምናምን እያለ የሚቀጥል ደብዳቤ ፅፎ ሰጠኝ፡፡ ክፍያ ነበረው - ሦስት ኒያላ ገዛሁለት፡፡ ስንቀጠቀጥ ሰነባበትኩና ወስጄ ሰጠኋት፡፡ ከጓደኞቿ ጋ ሆና (ምናለ ብቻዋን ሆና ብታነብበው - የሰጠኋት የግሌን ሕመም) አንብበው ሲያበቁ መውረጃ በሌለው የሳቅ አንቀልባቸው አዘሉኝ፡፡
አስጨነቁኝ፡፡ መግቢያ ቀዳዳ አሳጡኝ፡፡ ሳቃቸው የደረስኩበት ይደርሳል፡፡ የረገጥኩበት - ቀድሞኝ አለሁ ባይ ሆነብኝ፡፡ የምገባበት ሲጠፋኝ --- እቤቴ ገብቼ ግጥም ፃፍኩ፡፡
እኔስ መሞቴ ነው ባንቺ የተነሳ
የምን ሰው ገጠመኝ ጥይት የማይበሳ … (ው)
ያኔ ቤት የማይመታ ግጥም መጻፍ የሚቻል አይመስለኝም ነበር፡፡
 “ው” የምትለዋን ፊደል የጨመርናት ለዚህ ፅሁፍ ማሟያ ከደራሲው ጋር ተመካክረን ነው፡፡
ዛሬ አድጌያለሁ… ብያለሁ፡፡
ሀገር ስሜን የሚጠራው --- የተመሰገነ የግጥም ፋብሪካ ሆኛለሁ፡፡ ዛሬ እቤቴ ለምትመላለስ እማወራዬ ደብዳቤ አልፅፍም -- ሰማይም ሀገሯ አይደለም፡፡ ሀገሯ አዲስ አበባ - ላስፋው ካለች ኢትዮጵያ ነው -- ጨረቃም አይደለች --- ሴት ሆና በየቀኑ ሌላ ሰብዕና የምትይዝ ራሄል ነች -- የከዋክብት ቀርቶ የሰው አሽከር የላትም፡፡
ምን ባድግ -- ምን ሀገር ስሜን ቢጠራ -- ምን ደብዳቤ ባልፅፍላት --- ምንም እንኳን - እሷን ሳይሆን በሽታዋን መነሻ አድርጌ (በበሽታዋ ንሸጣ) -- ከሷ በዘለለ ሁናቴ ለአጠቃላዩ የሰው ልጅ (በሰው ልጅ ቋንቋ ሁሉ እፅፍ ይመስል) የሚናገረው አንዳች ነገር ያለው ግጥም ልወልድ ብችልና - በእውቅናዬ ብርሃን ላይ - ሌላ አንድ አዲስ ችቦ ማንቦግቦግ ብችልም ቅሉ -- መጨነቄን ግን አልክድም፡፡
ራሄል ጉዲት - በጡቷ ወሬ -- በዝባዝንኬ ካንሰሯ -- በሞት መጣ ሰበካዋ ምናምኔም ሳይቀራት በጭንቀት ሰቅዛ ይዛኛለች፡፡  እንግዲህ - መሄጃ ሁሉ ቢበዛ መዳረሻው አንድ ከሆነ -- ስንጀምር ያገኘነው - ስናጋምስ ካገኘነው - አጋማሹም ልናገባድድ ስንል ከምናገኘው በምን ይለያል? የሰባተኛ ክፍል ሁኔታዬም - የዛሬ አኳሃኔ -- መድረሻቸው ጭንቀት እስከሆነ ድረስ፤ የይዘትም ሆነ የቅለትና የክብደት ልዩነት የላቸውም፡፡ ምን አባቴ ላድርጋት!? ጨንቋታል - ፈርታለች - ግራ የሚያጋባ ዕልፍ ሰብዕናዋ ብን ብሎ ጠፍቶ - ልሙጥና የተጨነቀች ራሄል ሆና ከፊት ለፊቴ ተቀምጣለች፡፡ መኖር ግን እንዴት ያለ መጨረሻ አልባ -- ሁሉን መሸሸጊያ ዋሻ ቢሆን ነው? ውበቷን ዛሬ ብቻ ሳይሆን - ሁሌም ነበር… የምታውቀው፡፡ ከዛሬ በፊት መደሰቻዋ --- ሌላውን ማንበርከኪያዋ የነበረ ውበቷ፣ ዛሬ ስጋቷ - ዛሬ ሰቀቀኗ ሆኗል፡፡ እንዲህ እንደሚሆን ማናችንም አልጠረጠርንም፡፡
“… ሞት ለኔ አይገባኝም  --- እኔ መኖር እፈልጋለሁ --- እንዲህ በቀላሉ ሬሳ ልሆን? ለምን ሲባል!? ለምን ሲባል -!? ቆንጆ ነኝ - መኖር አለብኝ --- ከኖርኩ ደግሞ ከነሙሉ ውበቴ እንጂ - መጉደል የለብኝም -- ጡቴ መቆረጥ የለበትም -- ጡቴ ተሰልቦ - መክተፊያ ደረት ከሆንኩማ ምኑን ኖርኩት…?” ራሄል እያወራች ነው፡፡ ወሬዋ ግን ለኔ ሳይሆን ከፊት ለፊቷ ተቀምጦ ለሚያዳምጣት እግዜር እያወራች ነበር የሚመስለው፡፡ ጭንቋን ያወራችው -- አጠገቧ ተቀምጦ --- ግራ መጋባቷን የተነፈሰችለት - ሁሉን ቻይ የሆነው እግዜሩ --- የሆነ ነገር እንዲፈጥርላት የፈለገች ትመስላለች፡፡ አጠገቧ ሆኜ የማዳምጣት --- በጭንቋ ሰአትም ከጎና ያለሁት ግን እኔ ነኝ፡፡ ጭንቋን የተጋራኋት --- ለሚቆረጥ ጡቷ የሚሆን ማፅናኛ ለመውለድ ማጣፊያው ያጠረኝ - እኔ ነኝ፡፡ እኔም ሆንኩ --- ካጠገቧ ተቀምጦ የሚሰማት እግዜሩ --- የቱንም አይነት ፈጠራ ብትፈልግ የምንሰጣት አይነት አይደለንም፡፡ ሁለታችንም ፈጥረን ጨርሰናል፡፡ “… አየህ መኖር እየኖርከው እያለ ምንም ማለት ነው -- ቀላልና የሚያሳስብ አይደለም -- በተለይ --- እንደኔ ቆንጆ ሆነህ ከኖርከው… ሁሉ ሲመለከትህ ደስተኛ የሚሆን እየመሰለህ ከኖርከው --- መኖር ዝም ብሎ ከመኖር የዘለለ ነገር ያለው አይመስልህም --- ለካንስ እንዲህ አይነትም መልክ አለውና ታውቃለህ ---!? ሳያዘጋጅህ --- ሳያስጠነቅቅህ የሚያልቅ ነገር እንደ ኑሮ ምንም የለም” ለኔ እያወራች ለኔ አይመስልም ወሬዋ፡፡ አጠገቧ ተቀምጦ ለሚያዳምጣት እግዜሩ እያወራች ያለች ነው የምትመስለው፡፡ እንዴ--- እንዴ!! እኔ እሆን እንዴ እግዜር!? እኔ እሆን እንዴ --- ለዘመኔ መጀመሪያም ሆነ ፍፃሜ የሌለኝ እግዜር!? ስለ በሽታዋ ግጥም መፃፍ እንጂ ከበሽታዋ ልፈውሳት የማልችል እግዜሯ? ፈጠራዬ አንዴ መንጭቶ የደረቀ -- ዛሬ ላይ ከመፈብረክ ውጪ ሌላ ኪን የማላውቅ እግዜሯ እኔ እሆን እንዴ…!?
ብቻ --- ሁላችን እንዲህ ነን፡፡ ሲጨንቀን ማንነታችን የሚገለጥ - ጭንብላችን የሚወልቅ -- የሆነ ወደ ኋላ የሚተረተር --- የሚጐለጎል፡፡ የዛሬ ሕይወታችን ላይ… የሆነ መምጫው ላይ -- መኖር የማይደፍነው -- ራሳችንን አሳልፈን ሰጥተንለታል የምንለው ስራችን የማያክመው -- አጠገባችን ሆኖ የሚያዳምጠን እግዜር፣ የሚያጠግገው እንጂ ጨርሶ የማይሽረው -- አንዳች ሽንቁር የያዝን --- እንደያዝነውም ለማክተም የምንሮጥ ነን፡፡

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 13 December 2014 11:13

የትራንስፖርት ገጠመኝ

ወያላው    ተሳፋሪ! ተሳፋሪ!
አዲስ አባ በፈሪ

አባት    ምን ማለቱ ይሆን?
ልጠይቅ ምስጢሩን…
ደገመ አሁንም አምርሮ፣
ማንን ፈርቶ ቃል ጨምሮ፡፡
ምን ማለቱ እንደሆን ልጠይቀው ብዬ፣
ጠጋ እያልኩ እየፈራሁ እቃዬን አዝዬ፡፡

ወያላው    ግቡ! ግቡ! ፋዘር መኪናው ፈሪ ነው፣
ሰውም እየበዛ ሲሄድ ቀስ ብሎ ነው፡፡
አትጠራጠሩ በልኩ ይጭናል፣
ሹፌሩ ፈሪ ነው ቀስ ብሎ ይነዳል፡፡
መንገድ ላይ መንከርፈፍ ሁሌ ልማዱ ነው፣
ምናልባት - ምናልባት ነገ ቢገባ ነው፡፡

አባት       ስለዚህ ብሎ… ብዙ ሳያወራ፣
ካፉ ላይ ቀማሁት ይሄን ወሮበላ፡፡
ምን ማለትህ ይሆን? ግራ ገባኝ ባክህ፣
ማከላከልህ ነው ቋንቋ ማሳመርህ፡፡
ዞር በል ከበሩ - ሰው እጠይቃለሁ፣
ከአንተ ጋር ሳወራ - ጊዜ አቃጥያለሁ፡፡

ወያላፋዘር ይቅርቦ ለርሶ አዝኜ ነው፣
መኪናው ቀርፋፋ ነገ ቢደርስ ነው፡፡

አባትምን ታዝንልኛለህ - የትስ ታውቀኛለህ?
በጣም ነው የማዝነው ለካስ ደላላ ነህ፡፡

ወያላይኸው ሚኒባሱ - ፋዘር በዚሂዱ፣
ስለ ንግግሬ ብዙ አይናደዱ፡፡
ወዲያው ይደርሳሉ ካሰቡበት ቦታ፣

አባትብሎ ሳይጨርስ ይሄንን ወስላታ፣
በለው! በለው! አለኝ ወኔዬ መጣና፡፡
እሱ መቼ ፈርቶ ማንንስ አክብሮ፣
መለፍለፍ ቀጥሏል መሬት አቀርቅሮ፡፡

አሠለፈች አበበ ደሳለኝ
አዳማ (ናዝሬት)

Published in ጥበብ
Saturday, 13 December 2014 11:11

እስቲ ይሞክሩት

በዓለም ላይ ለመምህራን ከፍተኛ ደሞዝ የምትከፍል አገር ማናት?
በዓለም ላይ ከፍተኛ ዕዳ ያለባት አገርስ?
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር ሰራዊት ያላት አገር የትኛዋ ናት?
ብዙ ቢሊዬነሮች ያሉባቸው የዓለማችን ሦስት ከተሞች የትኞቹ ናቸው?
ሦስቱ የዓለማችን እጅግ     ሃብታም አገሮች እነማን     ናቸው?
============    
መልስ
1    ስዊዘርላንድ (በዓመት 68ሺ ዶላር) ኔዘርላንድ፣ ጀርመንና ቤልጂየም ይከተላሉ፡፡
2    አሜሪካ (15,940,978 ዶላር) እንግሊዝ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ይከተላሉ
3   ቻይና (2,285,000) ግብፅ በ10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
4   ሞስኮ (84)፣ ኒውዮርክ (62) እና ሆንግኮንግ (43)
5   ኳታር፣ ሉክሰምበርግ እና ሲንጋፖር (አሜሪካ በ6ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች)

Published in ጥበብ

            የአውቶብሱ አፍንጫ በተለምዶ አጠራር ደሴ መንገድን ይዞ ይምዘገዘጋል። በውስጡ ካቀፋቸው መንገደኞች በተጓዳኝ ከተሳፋሪው አይን የተሰወረ የሙት መንፈስ አብሮ እየተጓዘ ነው። በመንፈስ አይን አማላይ በሆነች ሴት አጠገብ ያንዣብባል። መንፈስ ለውብ ገላ ቦታ የለውም። ስጋ እና መንፈስ ለየቅል ናቸው። መንፈስ ስጋ ገፎ የጣለ እርቃን ነፍስ ነው። ለእርቃን ገላ ሳይሆን ለእርቃን ነፍስ ነው ቀልቡ የሚከጅለው፡፡ እርቃኗን ወደታየችው ሴት አጠገብ በሚገኘው አየር ላይ ማህለቁን ጣለ። ሴትየዋ በድሪዋ ተከናንባ ትተክዛለች። ከአጠገቧ የተቀመጠው ኮበሌ ከጨበጠው ጫት እንድትቀም እጁን ዘረጋላት። መቃም እንደማትፈልግ ጭንቅላቷን ግራ ቀኝ በማማታት ገለጸችለት። መንፈሱ ባለ ድሪዋ ውቧ ሴት ጭንቅ ጥበብ የምትልበትን ሀሳብ ለመሰለል ወደ ውስጧ ዘልቆ ገባ፡፡
“ቀምበጥ ነኝ፤ መልአከ ሞት የሚሰነዳዳብኝ ቀምበጥ፤ ኧረዲያ…..የትኛው ባለጠግነት ሊቀር ነው..ይልቅ የፈሪ ዱላውን ሳያሳርፍብኝ ማልጄ ልጀግንበት……….ይህ ሰባራ አውቶብስ እየተንቀጠቀጠ አልፈጥን አለኝ እንጂ………እኔማ.. ከወሰንኩ ሰንብቻለሁ።” እልህ እየተናነቃት ከንፈሯን እየደጋገመች ትነክሳለች፡፡
መንፈሱ የባለድሪዋን ሙግት  ማድመጡን ገታ አደረገና ወደ ራሱ ተመለሰ። ስጋ ለብሶ በምድር ለመጨረሻ ጊዜ የቆየበት 1966 ዓ.ም ታወሰው። በ“ሶሻሊዝም” ፍልስፍና ልቡ የጠፋበት ፣አለም ሁሉ በእጁ መዳፍ የተቀመጠች ያህል የተሰማው ጊዜ፤ የቁም-ሞትን ቀድሞ የምር-ሞትን የሞተበተ የአፍላ ዘመን፤ ፍልስፍናው ከሁለመናው ዘልቆ ገብቶ ብስባሽ ስጋውን ለአላማው ለመሰዋት ሲንደረደር ሲንቀዠቀዥ የነበረበት ቀውጢ ሰዓት፤ የልቡን መሻት አይታ ደረቱን ለመንደል ስትምዘገዝ የነበረች የጥይት ቀለሀ መልሳ መላልሳ በምናቡ መጣችበት። የባለድሪዋ የምር-ሞትን አጥብቆ መሻት ከእርሱ ገጠመኝ ጋር መንታ መሆኑ ደንቆታል።
አውቶብሱ እንደ እባብ እየተሳበ፣ ከደሴ መግቢያ አፋፍ ላይ ደርሷል። ሹፌሩ ያጎረሰው ካሴት እየተነፋነፈ የሚያወጣው ድምጽ ባለ ድሪዋንም መንፈሱንም ከገቡበት የሀሳብ ሰምጥ ውስጥ ጎትቶ አወጣቸው። አቀንቃኙ የደሴን ስም አንስቶ አይጠግብም፡፡ በዘፈኑ ውስጥ ያሉት ስንኞች በሙሉ በደሴ ተጀምረው በደሴ ነው የሚያልቁት፡-
ገራዶ ፈቀቅ በል ደሴን ልይበት
ፍቅር እና ሸማ ሲያልቅ አያምርበት፣
አይቻለሁ በአይኔ መች ቀረሁ በዝና
ከሀገርም ደሴ አለ ከወንዝም ቦርከና፣
ደሴ ግራር እንጂ አያበቅልም ጥድ
ፍቅር ለመጨረስ ያልታደልኩትን፣
ዜማው መንፈሱን በጊዜ ታንኳ አሳፍሮ በምድር ቆይታው ከአርባ ዓመት በፊት የታደመባትን ከተማ ዳግም እንዲጎበኛት በግብዣ አግደረደረው። አካል አልባ ሰውነቱን ከወዲህ ወዲያ አንከላወሰና እንደ ንፋስ ሽው ብሎ ከሹፌሩ ፊት ለፊት ከተደነቀረው መስታወት ላይ ተለጥፎ ከተማዋን ማማተር ጀመረ። በትልቅ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ በፍቅር የተቃቀፉ አረጋውያን ቤቶችን ለአይን የምትመግብ ርህሩህ ባልቴት ከተማ ሆነችበት፤ ከላይዋ ላይ የተከናነበችውን አዳፋ ኩታ  በተቀነቀኑላት ውዳሴዎቿ ጀቡና ሽር ብትን የምትል፣ ጎብኚውን የምታጥበረብር ባልቴት ሴት መስላ ታየችው፡፡
በአእምሮ አልባው ጭንቅላት አሰበላት፣ አወጣ አወረደ፤ በአንጀት አልባው ሆድ እቃው ሊያዝንላት ቢፈልግም አልቻለም።
ውቧ ሴት ሻንጣዋን ለመሸከፍ ስትንደረደር ተመስጦው ደፈረሰ። አውቶብሱ ወደ መነኻሪያ በሚወስደው ልብ አውልቅ መንገድ ላይ ከግራ ወደ ቀኝ ዥዋዠዌ እየተጫወተ፣ ከቅጥር ግቢ ውስጥ ሰተት በሎ ገባ። አዳር በደሴ፡፡
ልጅ እግሩ ሹፌር ማልዶ ለጉዞ ለመንቀሳቀስ የአውቶብሱን ጡሩንባ ከልክ በላይ እያስቧረቀው ነው። ተሳፋሪዎቹ በጉዞ ድካም የተጫጫናቸውን የማለዳ እንቅልፍ ለማባረር ደጋግመው እያፋሸኩ፣ ከአውቶብሱ ውስጥ አንድ በአንድ ተሞጀሩ። መንፈሱ የባለድሪዋን አካባቢ ጎብኘት አደረገ። የጎደለ ሰው የለም። ውቧ ሴት-የምር ሞት ናፋቂዋን ገርመም አደረጋትና፤
«እንዲህ በቀላሉ ፍንችር ማለት ይቻላል ብለሽ ነው። እኛም ስንት ዝተን ነበር መሰለሽ» አለ በመንፈስ ቋንቋ፡፡
ሌላ ባለተራን ለመሰለል ዙሪያ ገባውን ማማተር ፈልጓል፤ ከመስኮት አጠገብ የተቀመጠች ባልቴት ባለተራ እንደሆነች ገባው፤ ፈጥኖ ቀረባትና በላይዋ ላይ እያንዣበበ የውስጧን ትርምስ ለማድመጥ ሁለመናውን ተከለ፡፡
በአፏ የወጠረችው የጫት ተርዚና እንደ ቀፈት ተወጥሯል፤ ለራሷ ስለ ራሷ መላልሳ በውስጧ ታነበንባለች፤
“ሂድ.. እንግዲህ፤ አዚምን.. ሸረኛን… ሟርተኛን… ከጎጃችን… ከቀዬአችን.. አብርልን፤ ጣረሞትን…. መላአከ ሞትን.. በሩቁ…. ያዝልን፤ ማጀታችንን በተድላና ፍስሃ…… ሙላልን፤ ለንሰሃ.... ሳንበቃ…. ፈጥነህ… አትከውነን፤ አብሽር አቦ …» ምርቃቱን አሳረገች፡፡
በውስጧ ያጫጫሰችው ሃድራ ሲቆምና የሚቦርቅ ጨቅላ ወደ እርሷ ሲገሰግስ አንድ ሆነ። ከእናቱ እቅፍ እያፈተለክ የሚሯሯጠው ኩታራ፤ ሴትየዋ ያለችበትን አካባቢ ጸጥታ እያደፈረሰ አስቸገረ። ከትከት ብሎ ይስቃል። ይፈነድቃል። በተብታባ አንደበቱ ያገኘውን ያወጋል።
መንፈሱ ጨቅላውን ከላይ እስከ ታች ለመዳሰስ ወሰነ። ደባበሰው። ውስጡን በረበረው። ጓዳ ጓድጓዳውን አገላብጦ ሰለለው፡፡ በጨቅላው ውስጥ ምንም ነገር ሊቃርም አልቻለም። ውስጡ እንደ አንደበቱ አይደለም። ሆድ እና ጀርባ። ጸጥ ረጭ። የተወረረ ከተማ ይመስላል።
 በየተራ ሲያደምጥ በነበረው የውስጥ ሙግት የተነሳ ከደሴ በኋላ ያሉትን ጥቃቅን ከተሞች ሳያያቸው እንደ ዋዛ አመለጡት። የተቀረቱን ለማየት ራዳሩን በውጪው ላይ ተከለ። አንድ ሁለት እያለ ከተሞችን ይቆጥር ያዘ። ደንቆታል። ከተሞቹን አውቶብሱ ሲያልፋቸው አንድ ይሆናሉ። ሁሉም በትእዛዝ በአውቶብሱ ሽንጥ ልክ የተሰሩ ይመስላሉ። በጣም ሚጢጢዬ ከተሞች። አውቶብሱም ሽው። ከተሞቹም ሽው። በከተሞቹ ላይ እየተሳለቀ ብዙም ፈቀቅ ሳይል ድንገት አውቶብሱ እንደ መንገጫገጭ ብሎ ቆመ። የአውቶብሱ ጉዞን ለማስተጓጎል ሆን ብሎ ያቀደ የሚመስል የግመል ሰራዊት በአስፓልቱ ሆድ ላይ ተነጠፈ። የሰራዊቱ ቁጥር በስሌት አይገፋም። ስፍር ቁጥር ከሌለው የግመል ሰራዊት መካከል አንድ ባለ ሪዛም-ግመል በኩራት ይጀነናል። መንፈሱ በግመል ቋንቋ ይህንን ባለ ሪዛም ግመል ሊያናዝዘው በመስኮት ሽው ብሎ ወጣ።
“ጥያቄያችሁ ምንድን ነው?“ አለ መንፈሱ፤ ወደ ሪዛሙ ግመል ጠጋ ብሎ
“የአመጻው ፍሬ ነገር ወዲህ ነው፤ ይህንን ሁሉ የግመል መንጋ ያገተውን ጌታችንን ወግድ ለማለት የቆረጥንበት ቀን ዛሬ ነው። እንደ እድል ሆኖ እናንተን አገኘን”
“የእናንተ አመጽ ከመንገደኛው ጋር ምን ያይዘዋል?”
”በደንብ ይገናኛል እንጂ። ብቻችንን ጌታችን ላይ ለማመጽ የግመል ተፈጥሯችን አይፈቅድልንም”
“በዚህ ጎዶሎ አሳዳሪያችሁ ላይ ፊታችሁን ማጥቆር ነው የተሳናችሁ?”
“ያልተነካ ግልግል ያውቃል። ነጻነት ያለ ዋጋ አይገኝም። አሳዳሪያችንን ወግድ ብንል ለከርሳችን  አቤት ማን ይልልናል? እህል ውሃ ፍለጋ  ላይ ታች ልንዳክር? ይህ ከሚሆን ጠግቦ ባሪያ መሆን ይመረጣል”
”ምን የሚሉት ማምታት ነው። ጨለማና ብርሃን አንድነት የላቸውም። ይልቅ አሳዳሪያችሁን በሻኛችሁ……… ” መንፈሱ ንግግሩን ሳይጨርስ የደነበረ በሬ የግመሎቹን አሳዳሪ መቀመጫ ሰቅስቆ ወደ ላይ ሲያጎነውና የተነጠፈው የግመል መንጋ ወደ የአቅጣጨው ሲበተን አንድ ሆነ፡፡
አውቶብሱ ተንቀሳቀሰ። ተሳፋሪው በሁኔታው ግር ተሰኝቷል፡፡ “አይ የ8ኛው ሺ ግመል ……” የሚል ደምጽ ከመንፈሱ ጆሮ ድንገት ጥልቅ አለ። ቃሉን ያወጡት ሹፌሩ አካባቢ ያሉ አዳፋ ቀሚስ የለበሱ አዛውንት ናቸው። ለጉስቁልና እጅ ሰጥተዋል። ትንሽ እልፍ ብሎ ከፊታቸው ወዝ የሚቀዳ፣ ድሎት ዘልቆ የገባቸው፣ ጥቁር ካባ የተከናነቡ፣ ጺማቸውን ያጎፈሩ ጎልማሳ ሰው አሉ። እጃቸው ላይ በጣም ዘመናዊ ስልክ ይታያል። የስልካቸውን ስክሪን እየነካኩ ጌም ይጫወታሉ። በጌሙ በጣም ተመስጠዋል። መሀል መሀል ላይ ለሚደወልላቸው ጥሪ በስጨት እያሉ መልስ ይሰጡና መልስው ወደ ጌሙ ይተከላሉ፡፡ መንፈሱ ወደ ጎስቋላው አዛውንት ተሳበና የውስጣቸውን ትርምስ ማድመጥያዘ፤
«እንዲህም ተኩኖ የእግዚሀርን መንግስት መውረስ፤ ግድየለም  ይህ በጨዋታ፣ በአልባሌ የመንፈዝ ልምድህ ይጠቅምሀል፤ በገሀነብ ለዳቢሎስ በእሳት ላይ የመሄድ ትርእይት  ታሳያዋለህ፤» በውሳጣቸው እያጉተመተሙ ከፉኛ ተብሰለሰሉ፤ የአዛውንቱን ብሽቀት በሰማበት ቅጽበት መንፈሱ  መንፈሳዊ ፈገግታውን በአየሩ ላይ ለቀቀው  ።
ተረኛውን ለማሰስ ተነሳሳ። በመስኮት አሻግሮ ወደ ወጪ ይመለከታል። አውቶብሱ አላማጣ ጋ ሲደርስ ወደ መሖኒ የሚያስገነጥለውን መንገድ ይዞ ተፈተለከ።
 በመንገዱ ጠርዝ ባሻገር ባለው አውላላ ሜዳ ላይ የአቧራ ማእበል እየደጋገመ ይነሳል። የአቧራው ሱናሜ በአካባቢው ላይ ነግሷል። አቧራውን ለብሰው የሚሯሯጡ ጨቅላዎች፤ ተራራን ራስጌ ያደረጉ ትልልቅ ቋጥኞች፤ የደረሱ የበለስ ተክሎች፡፡ ሁሉንም በወፍ በረር ከግራ ከቀኝ ሽው ሽው እያለ በመስኮቱ አሻግሮ ጎበኛቸው፡፡ ስራ የፈቱ፤ ያለ ጭንቅ የተዘረጉ ብዙ አውላላ ሜዳዎችን እየቆጠረ ነው የመጣው፡፡ የሰው ብዛት ከእርሱ ዘመን በንጽጽር እጅጉንም እንዳልተጋነነ እርግጠኛ ሆኗል፡፡ ብዛቱ ቢያይልማ ጠጠር መጣያ አይገኝም ነበር።
አውቶብሱ መንገዱን እየገመሰ ከሆነ አቀበት አካባቢ ደረሰ። አቀበቱ ምጥ ሆኖበታል። የጣር ድምጽ እያሰማ ቀስ ብሎ ይጎተታል። አቀበቱን ጨርሶ ለጥ ባለው መንገድ ላይ ሲንደረደር መንፈሱን አንድ ክስተት ቀልቡን ያዘው።
ከሲታ በሬዎችን የጠመደ ኪሲታ ገበሬ አለታማውን መሬት ለማረስ ይታገላል። ከኋላው ዘር በእርቦ የያዘች ጎስቋላ ሴት ትከተለዋለች። የለበሰችው ቀሚስ በላይዋ ላይ አልቋል። መንፈሱ እንደ መረበሽም እንደ መደንገጥም አደረገው። ግና መንፈስ ነውና በቅጡ መረበሽም መደንገጥም አልቻለም።
መሬት ለአራሹ በብርቱ ሲያዜመው የነበረው መፈክር ነበር። የኑሮውም የሞቱም መንስኤ ከገበሬ ጋር የተቆራኘ ነው። ከገበሬ ተወልዶ ለገበሬ ሞተ። ጠብ ያለ ነገር ግን የለም። ከርሞ ጥጃ። ከጥጃ ፈቀቅ ያለ ትእይንት እስካሁን አላስተዋለም። አሮጌውን ማንነት እንዳስቀመጠው ነው። የዱሮው በሬ ቀለሙ እንኳን አልወየበም። ከዛሬ አርባ አመት በፊት በአደራ መልክ ያኖረው ድንቁርና ከእነ ፍጥርጥሩ  እንዳገኘው ሲሰማው፣ በሞት አለም ውስጥ እያለ ያመለጠው ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ሆነ። ድንገት እንደ እርጎ ዝንብ በህያዋን አለም ውስጥ ጥልቅ ብሎ  የተመለከታቸውየተቃርኖ ትእይንቶች ሰላሙን ተፈታትነውታል። ለሞት የምትጣደፈው ውቧ ሴት፤በምርቃት የማትጠረቃዋ ባለተርዚናዋ ሴት፤ጥድፊያ አልባ አለም ውስጥ የሰጠመው ህጻን፤ለስጋ ፊት የማይሰጡት ጎስቋላ አዛውንት፤ስጋን በብርቱ የጠገቡት ባለ ካባው ጎልማሳ። ሁሉም በተቃርኖው አለም ፈተና ውስጥ ወድቀዋል።
መንፈሱ ወደ ራሱ አለም ለመመለስ ተሰናዳ። ከህያዋን አለም ያገኘው ደስታ የለም፤ትካዜ ብቻ፤የሚተክዙ ከተሞች፤ የተከዙ ሜዳዎች ፤የተከዙ መንገደኞች። ሌላ ምንም የለም። የመንፈስ አለሙ ክፉኛ ናፈቀው። ሽው ሽው አለና በረዳቱ መስኮት በኩል ተፈተለከ። አውቶብሱም የሚተክዙ መንገደኞቹን እንዳቀፈ፣ የተራቆቱ ሜዳዎችን ከኋላው እየተወ መሄዱን ቀጠለ። የጉዞ መዳረሻውን እርሱም በከርሱ ውስጥ እንዳጨቃቸው ተሳፋሪዎቹ በእጅጉ ይናፍቃል።



Published in ጥበብ
Page 8 of 13