ከእለታት አንድ ቀን አንዲት ቀበጥ ልጅ ከእናቷና ከሴት አያቷ ጋር አብራ ትኖር ነበር፡፡ ከቀበጥነቷም በላይ የሥራ ዳተኝነቷ አስቸጋሪ ነበር፡፡
እናትና አያት ይወያያሉ፡-
አያት - እንደው የዚችን ልጅ ነገር ምን ብናደርግ ይሻላል?
እናት - እረ እኔም ከዛሬ ነገ እጠይቅሻለሁ እያልኩ ስፈራ ስቸርኮ ነው የቆየሁት፡፡ የአያት አንጀት ሆኖብሽ ስለምታቆላብሻት እንዳትቀየሚ ብዬ ታገስኩ፡፡
አያት - እረ የምን ቅያሜ ነው እሱ?
እናት - እንግዲያው ለምን ቁጭ አድርገን ነገረ-ስራዋ ሁሉ እንዳልጣመንና ከእንግዲህ ቤቷን ቤቴ ብላ በስነ ሥርዓት እንድትኖር እናስጠንቅቃት፡፡
አያት - አዎ፤ መቼም የሙት ልጅ ናትና አባቷ ከሞተ ወዲህ ሀዘኗም ብስጭቷም በዝቶቦታል ብለን ብዙ ታገስናት፡፡ አሁን ግን በዛ!
እናት - መብዛት ብቻ! ተንዛዛች እንጂ! ምግብ በልታ ውልቅ! ጠዋት የወጣች አገሩን ስታካልል ውላ መምጣት! እራቷን በልታ ክልትው!
አያት  አዲስ ሀሳብ አመጡ:-
“ቆይ እስቲ ዛሬ መቼም አዕምሮ አላት፡፡ ታስብበትና ወደ ቀልቧ ትመለስ ይሆናል”
እናት - ምን አድርገሽ ቀልብ እንዲኖራት ታደርጊያታለሽ?
ምን እናድርግ ትያለሽ?
አያት - ወደ አልጋዋ እንጠጋና ወለሉን እኔ ልጥረግ እኔ ልጥረግ እያልን እንጣላ፡፡ ለመጥረግ እንታገል፡፡ ስትነቃ ተዉት እኔ እጠርጋለሁ በማለት ይሉኝታ ይይዛትና ትነሳለች፡፡
እናት - በጣም ድንቅ ሃሳብ! በይ ነይ እንሂድ፡፡
እናትና አያት እንደተባባሉት፤ አንድ መጥረጊያ ለሁለት ይዘው፤
አያት - ተይ ዛሬ እኔ ነኝ የምጠርገው?
እናት - ምን ሲደረግ!? አንቺ አርፈሽ ቁጭ በይ!
አያት - አብደሻል ስንት ዘመን አንቺ ልትጠርጊ ነበርኮ?
እናት - አይሆንም አልኩ አይሆንም!
ትግሉ ቀጠለና ልጅቱ ነቃች፡፡
ከአልጋዋ ቀና አለችና፤
“ለምን ትረብሹኛላችሁ? ቤቱን ለመጥረግ ይሄን ያህል ትግል ምን ያስፈልጋል? አንዳችሁ ዛሬ ጥረጉ፤ አንዳችሁ ደግሞ ነገ ጥረጉ” ብላ ተመልሳ ተኛች፡፡
***
የሥራ ሥነምግባር መሰረቱ ግብረገብነት ነው፡፡ ለእናት ለአባት መታዘዝ ነው! ጥቃቅኖቹን ትዕዛዛት በማክበር ማደግ የእድገትን ቁልፍ መጨበጥ ነው፡፡
“አጓጉል ትውልድ
ያባቱን መቃብር ይንድ”
የሚባለው በዋዛ አይደለም፡፡ በጥንቱ ዘመን “ያልተቀጣ” “አሳዳጊ የበደለው!” የሚል ስድብና እርግማን ትልቅ ዋጋ ነበረው፡፡ በምርቃትም ደረጃ “ትምህርትህን ይግለጥልህ!” ማለት የምርቃት ሁሉ ምርቃት ነው፡፡ ከወላጅ ማክበር ወደ መምህር ማክበር፤ ከዚያም ወደ አለቃ ማክበር ማደግ፤ ለአንድ ወጣት ትውልድ ትልቅ እሴት ነው፡፡ እነዚህ እሴቶች የሀገር ባህል አይናቄ መሰረቶች ናቸው፡፡ የግብረገብነት ባህል ሲያዩት ወይም ሲያወሩት ቀላል፤ ሲመረምሩት ግን ጥልቅ ነገር ነው፡፡ የትምህርት ባህል፣ የሥራ ባህል፣ የአስተዳደር ባህል፣ የፖለቲካ ባህል፣ የኮሙኒኬሽን ባህል፣ የውይይት ባህል፣ የመቻቻል ባህል… የሁሉ ነገር መሰረት ናቸው፡፡
ዴቪድ ቦህም የተባለ ፀሀፊ፡-
“…በውይይት ሂደት መንቃት በተካፋዮቹ በተሳታፊዎቹ መካከል የሚፈጠር የትርጉም መረዳዳት ፍሰት ነው፡፡ በመጀመሪያ ተሳታፊው ሁሉ የየግሉን አቋም/ጐራ ይይዝና ይሄን ብለቅ ሞቼ እገኛለሁ ይላል፡፡ እያደር ግን ከየግል ደረቅ አቋም ይልቅ የወዳጅነት ስሜት የበለጠ እንደሚሆን እየታየ ይመጣል፡፡ ምንም አይነት የወዳጅነት ቀረቤታ ሳይኖር መግባባት ብቻ ድንቅ ባህሪ ይሆናል…” ይለናል፡፡
አንዳችም ልዩና መሰረታዊ ዓላማ ከጀርባው ሳይኖር ወዳጅነትን መፍጠር መባረክ ነው፡፡ ለሀገር ለወገን የሚበጅ እፁብ ነገር ነው፡፡ ስብዕና፣ ዕውቀት፣ ምጥቀተ-ህሊና፣ የጋራ-ቤትን ማፍቀር፤ መሰረታዊ መነሻዎችና ማደጊያዎች ናቸው፡፡ በተለይ ወጣቱ ከመሰረት ከንጣፉ እኒህን ጉዳዮች ማወቅና መገንዘብ መቻሉ ደርዝ ያለው ነገር ነው፡፡ መተሳሰብ፤ መወያየት፣ ማንበብና መናበብ፣ በሥርዓት መኖር፤ የጋራ ምጥቀተ-ህሊና (Consciousness) ያስፈልገዋል - የሀገራዊነት መሰረቱ ይሄው ነውና!
ወጣቱን ሳይዙ ጉዞ ምን ተይዞ ጉዞ ነው፡፡ ወጣቱ ሲባል ደግሞ ለትምህርት ዝግጁ የሆነው፣ ለመንቃት የሚተጋው ራሱን ምንጊዜም ለመለወጥ የሚታትረው፣ አርቆ ማስተዋል ጐዳና ላይ ያለው ነው፡፡ በእርግጥ አገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠር ካለብን ከቤተሰብ አስተዳደግ፣ ከትምህርት ቤት መታነፅ፣ ለአካለ - ሥራ መብቃት ጋር የተሳሰረ ወጣት ይዘን መሄድ ይኖርብናል፡፡
የዕውር የድንብር አለመሄድ ትልቁ ጥበብ ነው፡፡ ወጣቱ ህይወትን የሚቃኝበት ኮምፓስ ያሻዋል፡፡ ሌሎችን የሚማርክበት ማግኔት ያለው እንዲሆንም እንጠብቃለን፡፡ በዚህ የመረጃ ዘመን መረጃ - የለሽ ትውልድ እንዳይፈጠር ሁሉም ዜጋ አስተዋፅዖ ሊያደርግ ይገባል፡፡
የጥበብ ዐይኑ የተከፈተ ወጣት የበለፀገ ዕይታ ይኖረዋል፡፡ በኪነጥበብ እንዲጠነክር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በቅጡ ማወቅ የአንድ ህብረተሰብ የዕድገት ምልክት ነው፡፡ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ለዕለት - እንጀራ መፈለጊያ የሚበቃ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ምሉዕነት ያለው የዕውቀት ቀንዲል ለመጨበጥ እንዲነሳሳ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡
እጓለ ገብረ ዮሐንስ የተባሉ የአገራችን ደራሲ ስለአቴናውያን ሲፅፉ፤ “እሊህ አቴናውያን የነበራቸው አዲስ ነገር ለመስማትና ለመናገር መጓጓት ንጹሕ ሰብዓዊ ስሜት ነው፡፡ ወደፊት ለመራመድ የቻሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በማናቸውም የአውሮፓ ሥልጣኔ ክፍሎች ዘንድ የነሱን ማህተም ያልተሸከመ ነገር አይገኝም፡፡ ጫፉን ለመጥቀስ ያህል በሳይንስ ረገድ እነ ዲሞክሪቶስ እስከ አቶምፊዚክስ ድረስ የደረሱ ነበሩ፡፡ በፖለቲካ ድርጅት ረገድ እስከ ዲሞክራሲ የደረሱ ነበሩ፡፡ ለዚህ ሁሉ የሥልጣኔ ሀብታት መገኛ ለመሆን የቻሉት በንጹህ ሰብዓዊ ጠባይ እየተመሩ አዲሱን ነገር በመመኘት ስለዚያም በመናገርና በመስማት ነው” ይሉናል፡፡ አዲስ ነገር ለማየት የሚጓጓ ትውልድ ያስፈልገናል፡፡ ይህ ማለት ግን መነሻውን፣ ታሪኩን፣ ባህሉን፣ የዕውቀት ውርሱን በመመርመር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ “ማናቸውም የህሊና ተግባር በህገ - ምክንያት የተመሠረተ (Causalities) መሆን አለበት” ይሉናል የጠቀስናቸው ፀሐፊ፡፡
ብርሃናማ ነገ እንዲኖር ዛሬ ብርሃናማ ትውልድ የሚወራረሰው የጽሑፍም ሆነ የአፈ - ንግርት ቅርስ እንዲያፈራ፤ ምሁራን በተለይም ፀሐፍት የወጣቱን ዐይን ሊከፍቱለት ይገባል -በዚህ ረገድ የራሳቸውን መክፈልት ሊከፍሉ ይገባል፡፡ እንዲያው በደፈናው ትውልድን መራገም ማብቃት ይኖርበታል፡፡ ሃዋርያና ደቀመዝሙር መሆን አለባቸውና፡፡ ተቀምጠን ከምናላዝን ተንቀሳቅሰን ለነገ ለውጥ እናምጣ ነው ጉዳዩ! “የተቀመጠች ወፍ ሆዷን ስትዳብስ የበረረች ወፍ አፏን ትዳብሳለች” ማለት ይሄው ነው፡፡  

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የ25 ዓመቷ አሜሪካዊት ጄድ ሲልቪስተር፤ በእርግዝና ወቅት በተፈጠረባት አምሮት መላቀቅ ዳገት ለሆነባት ክፉ ልማድ እንደተጋለጠች ትናገራለች፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ነፍሰጡር ሳለች የጀመረችው የመፀዳጃ ቤት ወረቀት (ሶፍት) የመብላት ልማድ ከወለደችም በኋላ ሊላቀቃት አልቻለም፡፡ ዛሬ ያ አምሮት ወደ ሱስ ያደገ ይመስላል፡፡ በየቀኑ አንድ ጥቅል ሶፍት ታነክታለች፡፡
“ባረገዝኩ በሁለተኛ ወሬ ነው ሶፍት የመብላት አምሮት (ፍላጐት) ያደረብኝ፡፡ ለምን እንደሆነ ግን አሁንም ድረስ አላውቀውም፡፡
 ከጣእሙ ይልቅ ደስ የሚለኝ ሻካራነቱ ነው፡፡ ደረቅነቱን እወደዋለሁ” ያለችው ጄድ፤ “ቤተሰቦቼ ለጤናዬ ጥሩ አለመሆኑን ይነግሩኛል፤ ነገር ግን ለመተው አልቻልኩም” ብላለች፡፡
ልጇን ከተገላገለች አንድ ዓመት ከሦስት ወር ያለፋት ቢሆንም መፀዳጃ ቤት ገብታ በተቀመጠች ቁጥር ሶፍት እየቀረደደች መብላቷን ገፍታበታለች፡፡ በየቀኑም አንድ ሙሉ ጥቅል ሶፍት እንደ ምግብ አኝካና አጣጥማ እንደምትውጥ ተናግራለች፡፡ ነፍሰጡር ሳለች መፀዳጃ ቤት ገብታ ጥቅል ሶፍት ስታይ “ይሄንን መብላት አለብኝ” እያለች ትጐመዥና ትመኝ እንደነበር ያስታወሰችው ጄድ፤ ዛሬ ግን አንዳንዴ ወደ መታጠቢያ ከመሄድ ሁሉ ራሷን እንደምታቅብ ገልፃለች፡፡ “ምክንያቱም ከሄድኩኝ መብላቴ አይቀርም፡፡ ሽንት ቤት በሄድኩ ቁጥር ወደ 8 ገደማ የሶፍት ቁራጮች እበላለሁ አንዳንዴም ሶፍቱን ለመብላት ስል ብቻ መፀዳጃ ቤት ለመሄድ እገደዳለሁ” ትላለች፡፡
ለመብላት የምትመርጠውን የሶፍት አይነት ስትናገር ደግሞ፤ ከውዶቹ ይልቅ በየሱፐርማርኬቱ የሚገኙት ተራና ርካሽ ሶፍቶች ምርጫዋ እንደሆኑ ገልፃለች፡፡
“የተለያዩ የሶፍት ምርቶች የተለያየ ጣእም አላቸው፤ በመፀዳጃ ቤት ውስጥ አንድ ጥቅል ለምበላው፣ አንድ ጥቅል ደግሞ ለተለመደው አገልግሎት አስቀምጣለሁ” ብላለች ጄድ ሲልቪስተር፡፡ የመጨረሻ ወንድ ልጇን ከተገላገለች ጊዜ ጀምሮ (16 ወራት ገደማ ማለት ነው) ሶፍት መብላቷን ለመተው ብዙ ታግላለች፤ ሆኖም አልተሳካላትም፡፡ ልጅ ከወለድኩ በኋላ አምሮቱ የሚተወኝ መስሎኝ ነበር ያለችው ጄድ፤ ነገር ግን ሶፍት መብላቴን ላቆም አልቻልኩም ትላለች - ተስፋ በቆረጠ ቅላፄ፡፡
“ሶፍት መብላቴ ለሰውነቴ መልካም ሊሆን እንደማይችል አውቃለሁ፤ እስካሁን ግን ምንም የጤና ችግር ወይም ህመም አላስከተለብኝም” ያለችው ሚስ ሲልቪስተር፤ ሶፍት ስትበላ ልጆቿ እንዳያዩዋት ለመደበቅ እንደምትሞክር ገልፃ ድንገት ካዩዋት ግን እንደሚቆጧት ተናግራለች፡፡ ጄድ ሲልቪስተር የአምስት ልጆች እናት ናት፡፡ የአገራችን ሰው “አያድርስ ነው” የሚለው ለካ ወዶ አይደለም!!

Published in ዋናው ጤና

          ቅዳሜ ምሽት ነው አራት ሰዓት ገደማ፡፡ አልጋዬ ላይ ጋደም ብዬ “አንድ ለእናቱ” የሆነውን የቴሌቪዥን ጣቢያ እየተመለከትኩ ነው- የቀድሞውን ኢቴቪን የአሁኑን ኢቢሲን፡፡ ብዙውን ጊዜ ጣቢያውን የመመልከት ፍላጎቱ የለኝም፡፡ በፊት በፊት ቢያንስ ዜና እና የመዝናኛ ፕሮግራሞችን አልፎ አልፎም ቢሆን እመለከት ነበር፡፡ በኋላ ግን ተውኩት፡፡ ምክንያቴ ደግሞ ጣቢያው ለእኛ ለተመልካቾቹ መረጃን እና ፕሮፖጋንዳን ለይቶ ማቅረብ አለመቻሉ ነው፡፡ “ማር የላሰ ጠላ” እንደሚባለው ነው፡፡ ፕሮፖጋንዳ የላሰ መረጃ!
ዛሬ ምሽት ግን አጋጣሚው አሳልፎ ሰጥቶኝ አይኖቼ በጣቢያው በመተላለፍ ላይ ያለን አንድ ፕሮግራም እየተመለከቱ ነው፡፡ ፕሮግራሙ የቀጥታ ስርጭት ነው- “የህዳሴው ድልድይ” እየተገነባ ካለበት ከጉባ፡፡ እውነት ለመናገር እየተላለፈ የነበረው ፕሮግራም በብዙ መልኩ አስገራሚ ነበር፡፡ ሽር ጉዱና የተሰጠው ትኩረት “ሁሉም ነገር ወደ ጉባ” የተባለ ይመስላል፡፡ በምሽቱ በጉባ “የብሔር ብሔረሰቦች ቀን” የዋዜማ በዓል እየተከበረ ነው፡፡ ፕሬዘዳንቱን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም በሥፍራው ታድመዋል፡፡ መች እነሱ ብቻ- አርቲስቶች፣ የግድቡ ግንባታ ሠራተኞች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት… በርካታ ህዝብ በቦታው ታድሟል፡፡ የዋዜማውን ፕሮግራም እየመሩ ያሉት አራት የሚደርሱ አርቲስቶች በየደቂቃው እየተቀባባሉ ዘጠነኛው “የብሔር ብሔረሰቦች ቀን” በዓል ዘንድሮ እየተከበረ የሚገኘው “ሕገ መንግስቱ” ከጸደቀበት ሀያ ዓመት ጋር በአንድ ላይ በመሆኑ፣ እንዲሁም “የህዳሴው ግድብ” ግንባታ እየተካሄደ በሚገኝበት ቦታ ላይ በመከበሩ “ልዩ” መሆኑን (ልዩ ያልሆነ ነገር የሌለን አይመስልም) ይገልጻሉ፡፡ ለበዓሉ የተሰጠው ትኩረት እያስገረመኝ በመቀጠል ላይ ያለውን ፕሮግራም መመልከቴን ቀጠልኩ፡፡
የመንግስት ሹማምንቱ ወደ መድረኩ እየተጋበዙ በዓሉን በተመለከተ “መልዕክት” ነው ያሉትን ያቀርባሉ፡፡ “አርቲስቶቻችን” ይዘፍናሉ፤ ታዳሚው ይጨፍራል፡፡ ጉባ ላይ ደማቅ ቀትር እንጂ ውድቅት አይመስልም፡፡ ምሽት ሆኖ ሌሎች ከተሞቻችንን የተሰናበተችው ፀሐይ ጉባ ላይ በሙሉ ኃይሏ የከተመች ትመስላለች፡፡
መመልከቴን እንደቀጠልኩ ቢሆንም አንድ ነገር ግን ውስጤን እየኮሰኮሰው ነው፡፡ በዓሉ “የብሔር ብሔረሰቦች በዓል” መሆኑን የፕሮግራሙ መሪዎችና ባለስልጣናቱ ደጋግመው ከመወትወታቸው ውጪ ክንውኑ ላይ ያንን የሚያስረግጥ ቀለምና መንፈስ አጣሁ፡፡ ለምን?! ወይስ ለፕሮፖጋንዳው ትኩረት ሲሰጥ ሌላው ሌላው ጉዳይ ተዘነጋ?! ወይስ…..? እየተባለ ያለውና እየሆነ ያለው የምድርና የሰማይ ያህል ተራራቀብኝ፡፡ እናም ያልተቋጨውን ፕሮግራም መመልከቴን አቋርጬ ትኩረቴን ተገልጦ ጉልበቴ ላይ የተዘረጋው መጽሐፍ ላይ አደረግሁ፡፡“ነገርን ነገር ያነሳዋል” እንዲሉ አበው፣ እዚህ ጋ ዘወትር ግራ የሚያጋባኝን አንድ ነገር ላንሳ፡፡ ምናልባት የህግና የስነ ማህበረሰብ ባለሙያዎች ግልፅ ሊያደርጉልኝ ይችሉ ይሆናል፡፡ አንድ ቃል አለ በተደጋጋሚ የሚነገርና የሚሰማ- “ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” የሚል፡፡ እንደ እኔ ይህንን ቃል እንዲሁ እንቀበለው ካላልን በቀር ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ “ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” ማለት ምን ማለት ነው? የትኛውን ፅንሰ ሀሳብስ ነው የሚፈታው?  “ብሔር” ስንል ምን ማለታችን ነው? “ብሔረሰቦች”ስ? በ“ብሔር”ና በ“ብሔረሰቦች” መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? በ“ብሔረሰቦች”ና በ“ህዝቦች” መካከልስ?... “ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” ስንል ምን ማለት ነው የምንፈልገው? እውነት ቃሉ ፅንሰ ሀሳቡን ይወክላል? አይመስለኝም፡፡ ስላልመሰለኝም እጠይቃለሁ፡፡ መጠየቅ መብት አይደል!
ሰኞ ጠዋት “የእለት ጉርሴን እና የዓመት ልብሴን” ለማግኘት ከቤቴ ስወጣ አይኔ ብዙም ያልተለመዱ ነገሮችን አየ፡፡ በርካታ ህጻናት የተለያዩ ብሔረሰቦችን ልብስ ለብሰውና በወላጆቻቸው እጃቸውን ተይዘው በመንገድ ላይ አለፉኝ፡፡ የዘንድሮው “በዓል” ከበድ እንዳለ ቀልቤ እየነገረኝ ነው፡፡ ከየትና እንዴት እንደተከሰተ ያላወቅሁት ጥያቄ አእምሮዬን ሰቅዞ ያዘኝ፡፡ እንዲህ የሚል “እነዚህ ህጻናት የየትኛውን ብሔረሰብ ልብስ ነው የለበሱት?” ወይንም “ወላጆቻቸው ህጻናቱን የየትኛውን ብሔረሰብ ልብስ ነው ያለበሷቸው?” አእምሮዬ ምላሽ ፍለጋ ቃተተ፡፡
ይህንን እያሰላሰልኩ ሳዘግም አንድ በጥቂቱ የምንግባባ ወዳጄን ከፊት ለፊቴ ሲመጣ አየሁት፡፡ ህጻን ልጁን በእጁ ይዞ በፍጥነት እየተራመደ ነው፡፡ ህጻኑ ላይ አይኔ አረፈ፡፡ የአንድ ብሔረሰብን (የእከሌ ማለቱን አልፈለግሁም፡፡) የባህል ልብስ ለብሶአል፡፡ አባትና ልጅ አጠገቤ ደረሱ፡፡ ወዳጄን ሞቅ አድርጌ ሰላም ካልኩት በኋላ በእርጋታ አንድ ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡
“ልጅህን ወዴት እየወሰድከው ነው?”
“ወደ ትምህርት ቤት” አለኝ ፈጥኖ፡፡ ቀጠለናም “ዛሬ የብሔረሰቦች ቀንን ያከብራሉ” አለኝ፡፡
ብዙም ሳያደክመኝ ለጥያቄዬ ስለተመቻቸልኝ እየተደሰትኩ የምፈልገውን ቀለል አድርጌ ጠየቅሁት፡፡ “ታዲያ የማንን ብሔረሰብ ልብስ አለበስከው?”
ከብርሃን ፈጥኖ በኩራት መለሰልኝ፡፡ “እንዴ ምን ማለትህ ነው፤ የራሴን ነዋ፡፡” ለጥያቄዬ መልስ ለማግኘት የደከምኩትን ያህል መልሱን ስሰማ አልተደሰትኩም፡፡
“እናም ልጅህ ገና ከአሁኑ የራሱን ብሔር አወቀ ማለት ነዋ” አልኩት፡፡ ወዳጄ ፊት ላይ ቅሬታና ድንጋጤ ተቀላቅሎ አነበብኩ፡፡ እንዲህ እንደሚሆን ያሰበው አይመስልም፡፡
አሁንም እያዘገምኩ ነው፡፡ በርካታ ወጣት እህቶቻችንን እና እናቶቻችንን እንዲሁም ጥቂት ወንድ ጎልማሶችን የተለያዩ ብሔረሰቦችን አልባሳት ለብሰው በመንገዴ ላይ ተመለከትኩ፡፡ ሁኔታው ካለፉት ዓመታት “የተለየ” መሆኑ (ምክንያቱን የሚያውቁት አዘጋጆቹ ናቸው) ለበዓሉ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን የሚያሳይ ነው፡፡ የሆነውም እንደዚያ ነው፡፡ በዕለቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ በመንግስት መስሪያ ቤቶች የስራ ቀን አልነበረም፡፡ በትምህርት ቤቶችም እንደዚሁ፡፡
“የብሔር ብሔረሰቦች በዓል”ን ማክበር በራሱ ችግር ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ከፍተኛ ጥንቃቄን እንደሚፈልግ አምናለሁ፡፡ የሚያተርፈው እና የሚያከስረው ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ሊጠየቅና በቂ መልስ ሊያገኝ ይገባል፡፡
የበርካታ ብሔረሰቦች መኖሪያ በሆነችው ሀገራችን የተለያዩ ብሔሮች መኖር የጀመሩት አሁን አይደለም፡፡ አብረውና ተከባብረው ሲኖሩ ዘመናት አልፈዋል፡፡
ይህ ከሆነ ታዲያ አሁን ምን ለማትረፍ ነው ይህ በዓል ያስፈለገው? ከሁሉ በፊት የበዓሉ መከበር እንደ ሀገር የሚሰጠው ትርፍ በቅጡ ሊሰላ ይገባል፡፡ በአከባበሩ ላይ ያሉ ሂደቶችና ሁኔታዎች ሊፈጥሩ የሚችሉት አደጋም ሊጠና ይገባል፡፡ አሁን የተያዘው አከባበር ላይ አደጋ ይታየኛል፡፡ ሊያውም ለነገ የሚተርፍ ግዙፍ አደጋ!
ልብ በሉ! በበዓሉ ቀን ሰዎች የ“የብሔረሰባቸውን” ልብስ ለብሰው ከቤታቸው ይወጣሉ፡፡ በበዓሉ መከበሪያ ቦታ ላይም “የራሳቸውን” ብሔረሰብ ጭፈራ ይጨፍራሉ፡፡ አጋጣሚውንም ካገኙ ስለ ብሔረሰባቸው ታላቅነት ይናገራሉ፡፡ የዚህ ትርፉና ውጤቱ ምንድነው? አንድነት፣ አብሮነት፣ መከባበር… ወይስ ውድድር፣ መቧደንና እኛ እንዲህ ነን ማለት! በተለይ ደግሞ ህጻናት በዚህ ሂደት ውስጥ ሲያልፉ ዘመን አልፎ የሚፈጠረውን ሀገራዊ ቀውስ አስቡት፡፡ የምናስተምራቸው ሌሎች በርካታ ነገሮች የሌሉ ይመስል አንድ ቀን እንኳን ስለ ብሔራቸው ምንነት አስበውና ጠይቀው የማያውቁትን ህጻናት “ብሔራችሁ ይሄ ነው!” ብለን እንነግራቸዋለን፡፡ የዋህና ንጹህ የሆኑትን ልጆች ራሳቸውን ከጓደኛቸው ለይተው እንዲመለከቱ መንገዱን እያሳየናቸው ነው፡፡ ከዚያስ እነዚህ ህጻናት ራሳቸውንም ሆነ እኩዮቻቸውን የሚያዩበት አይን ምን ይሆናል? ምን አይነት ዜጋ ነው የምንፈጥረው?!
እርግጥ ነው በዚህ አጋጣሚ በሀገራቸው የተለያዩ ብሔረሰቦች እንዳሉና የተለያየ አለባበስ፣ ጭፈራና ቋንቋ እንዳላቸው ለማወቅ እንድሉን ያገኙ ይሆናል፡፡
 ሆኖም ግን በዚህ አይነቱ ሂደት የቱ ነው የሚያመዝነው? ትርፉ ወይስ ኪሳራው? ጥቅሙ ወይንስ ጉዳቱ? አደጋው የታሰበበት አይመስልም፡፡ ወይንም ቸል ተብሎአል፡፡ ደግሞም ፍቅርን፣ መከባበር እና መተባበርን በህዝቦችና በትውልድ ላይ ማሳደር የሚቻለው አንድ ቀን ተከብሮ በሚያልፍ በዓል አይመስለኝም፡፡ የምር የምንፈልግ ከሆነ መንገዱ ሌላ ነው፡፡ ሌላ!
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዚችው ሀገራችንና በህዝቦቿ እየተከበሩ ያሉ በርካታ በዓላት አሉ፡፡ በበዓላቱ ስያሜዎችና መከበር ላይ ተቃውሞ የለኝም፡፡ ሆኖም ከጥድፊያና ከአንድ ቀን ሰበካ ባለፈ የምር የሆነ ነገር ስለማላይባቸው ትርፋቸው ያሰጋኛል፡፡
ከተራ የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ባለፈ ዓላማቸው ምንድን ነው? ትርፋቸውስ? የሚያመጡት የጎንዮሽ ጉዳትስ?... የመሳሰሉት ነገሮች ትኩረት አልተሰጠባቸውም፡፡
የዚህ ሁሉ ምክንያቱ በጉዳዩ የምር ሳናምንበት ስለምናደርገውና ምናልባትም አላማችን በአደባባይ ከምንለው የተለየ ስለሆነ ይሆናል፡፡ ይሄ የእኔ ግምትና ስጋት ነው፡፡ የተለየ ሃሳብ ያለው ቢያጋራኝ ደስታውን አልችለውም፡፡
መልካም ሰንበት!!


           ዓምና በጅጅጋ በተከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ላይ ቀጣዩን 9ኛ በዓል የቤኒሻንጉል ክልል ርዕሰ መዲና አሶሳ እንድታስተናግድ ስትመረጥ፣ ከታዳጊ ክልልነቷ አንፃር እንዴት ይቻላታል የሚል ስጋት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሆኖም የክልሉ መንግስት ከግል ባለሃብቶች ጋር ተቀናጅቶ ወደ 5 ሺህ የሚጠጉ እንግዶችን ማስተናገድ ችሏል፡፡ በአሉ የሚከበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚገነባበት ክልል እንደመሆኑ የእንግዶች ቁጥር ከተገመተው በላይ ነበር፡፡
በአጠቃላይ 3577 እንግዶች በበአሉ ይሳተፋሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ከ1 ሺህ በላይ ያልተጠበቁ እንግዶች በበአሉ ታድመዋል ተብሏል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የክልሉ መንግስት በአሉን በጋራ ያዘጋጁት በመሆኑ በተናጥል የቀረበ የበጀት ሪፖርት ባይገኝም የክልሉ መንግስት ነባር መንገዶችን ለመጠገንና ለማደስ እንዲሁም የማስዋብ ስራ ለመስራት ወደ 11 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
የአሶሳ ብሄራዊ ስታዲየም በሼክ መሃመድ አላሙዲ ድጋፍ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ለበአሉ እንዲደርስ ተብሎ የተገነባ ሲሆን የግል ባለሃብቶችም በዘመቻ መልክ ለእንግዶች ማረፊያ የሚሆኑ ፔንሲዮኖችንና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ገንብተዋል፡፡ ከአመት በፊት አሶሳን ያውቃት የነበረ አንድ ወዳጄ ፤ ከተማዋ ጥሩ ማስተር ፕላን ቢኖራትም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በጥራትም በብዛትም አልነበራትም ብሎኛል፡፡ መንገዶቹ ከፊል አቧራማ እንደነበሩም ያስታውሳል፡፡ ለበአሉ ሲባል በተሰራው ስራ ግን ሙሉ ለሙሉ የከተማዋ ገፅታ መቀየሩን ይኸው ወዳጄ ይመሰክራል፡፡ በተለይ የመንገዶች ማስፋፊያና ዋና ዋና አደባባዮችን የማስዋብ ስራ የከተማዋን ገጽታ ፍፁም ቀይሮታል፡፡  
አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎችም አንቀላፍታ የነበረችው አሶሳ በብሄር ብሄረሰቦች በአል ምክንያት መነቃቃት መጀመሯን መስክረዋል፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች በአልን ደግሞ ደጋግሞ ያምጣልን ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ክልል በአሉን ለማክበር 10 ኮሚቴዎችን አዋቅሮ ሲሰራ እንደከረመ “አወደ-ቤጉ” የተሰኘው የክልሉ ልሳን ጋዜጣ ይጠቁማል፡፡ ኮሚቴዎቹ የከተማዋን ባለሃብቶች በማስተባበርም የመስተንግዶ ስራውን ያከናወኑ ሲሆን ባለሃብቱ ለበአሉ አጠቃላይ 4 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ማዋጣቱን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
“የምግብ እና የመጠጥ ኮሚቴ” የአቅርቦቱንና የመስተንግዶውን ጉዳይ ለአንድ የሽርክና ማህበር እንደሰጠ የጠቆመው ጋዜጣው፤ ማህበሩም በ6 ቦታዎች የምግብ ማብሰያ ጣቢያዎችን በማቋቋም ሲተጋ ሰንብቷል፡፡ ለበአሉ 100 ኩንታል ጤፍ የተዘጋጀ ሲሆን በየቀኑ እስከ 15 የሚደርሱ በሬዎችን 120 በጐች እንዲሁም እስከ 250 የሚሆኑ ዶሮዎችን ለእርድ ቀርበዋል፡፡የሽርክና ማህበሩ ለ2955 እንግዶች ምግብና መጠጥ ያቀረበ ሲሆን ወጪውን የሸፈነው የክልሉ መንግሥት የፌዴሬሽን ም/ቤት ነው፡፡ የ622 እንግዶችን ወጪ ደግሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት እንደሸፈነ ተጠቁሟል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን በበአሉ ማጠናቀቂያ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ም/ቤቱ ከገመተው በላይ እንግዶች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
እንግዶች በተለያዩ ቦታዎች ያደሩ ሲሆን ለየብሄረሰቡ የባህል ትርኢት አቅራቢዎች በአሶሳ ዩኒቨርስቲ ለጋዜጠኞችና ለኪነጥበብ ባለሙያዎች በአሶሳ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መኝታ ተዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡ ሆኖም አብዛኛው ጋዜጠኛ በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ሆቴሎች እንዲያድሩ ተደርጓል፡፡
በዚህ መልኩ እንግዶቿን ያስተናገደችው አሶሳ፤ 10ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች በአል የማዘጋጀት ኃላፊነቱን ለጋምቤላ አስረክባለች፡፡ የጋምቤላ ርእሰ መስተዳድር ባደረጉት ንግግርም፤ “በ10ኛው በአል ላይ የተሻለ መስተንግዶ ጠብቁ” ሲሉ ከወዲሁ ቃል ገብተዋል፡፡
ጥቂት ስለ ህዳሴው ግድብ
የህዳሴው ግድብ ግንባታ 40 በመቶ መድረሱ የተገለፀ ሲሆን ከመሬት  ከአንድ እግር ኳስ ሜዳ በላይ በሆነ ውፍረት 60 ሜትር ከፍታ ላይ ደርሷል፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ 145 ሜትር ከፍታ የሚኖረው ሲሆን በ10 ተርባይኖች 6ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከ270 ካሬ ኪ.ሜ በላይ ስፋት ያለው ሰው ሰራሽ ሃይቅ እንደሚፈጠርም ታውቋል፡፡ የበአሉ ታዳሚዎች ህዳር 27 ቀን ግድቡን የጎበኙ ሲሆን አዳራቸውን እዚያው ነበር ያደረጉት፡፡ በእለቱ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ተገኝተው ነበር፡፡ የህዳሴው ግድብ በ24 ሰአታት ውስጥ 16.949 ሜትር ኪዩብ አርማታ በመሙላት በቻይና ተይዞ የቆየውን የግንባታ ሪከርድ እንደሰበረ መገለፁ ይታወሳል፡፡
የአልበሽር ጉብኝት
የአሶሳ ስታዲየም ህዳር 29 ቀን በተከበረው የብሔር ብሄረሰቦች በአል ላይ  ሞቅ ያለ አቀባበል የተደረገላቸው የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር፤ ከሰአት በኋላ በህዳሴው ግድብ ያልተጠበቀ ጉብኝት  አድርገዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌም የተገኙ ሲሆን ጉብኝቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ ካሳ ተ/ብርሃን ተናግረዋል፡፡
 አልበሽር ባደረጉት ንግግርም፤ መንግስታቸው ለግድቡ መገንባት  ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የሃገራቸው ህዝብም በግድቡ ግንባታ ደስተኛ መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡      

ወጣቶች በ”አንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” አልመዋል

     በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ስር የሚገኘውና በተለምዶ “አላሙዲን ያጠረው” እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ለአመታት በሽንት፣ በሰገራና በመጥፎ ሽታ ተበክሎ ብዙዎችን ለበሽታ ሲዳርግ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለትና ሶስት ወራት ወዲህ ግን አካባቢው በመጠኑም ቢሆን እየተለወጠ መጥቷል፡፡
ፒያሳ  መንገድ ላይ ለሚሸኑ መንገደኞች ፖፖ በማቅረብ “እናንተ ወደ ፖፖው ካልሄዳችሁ፣ ፖፖው ወደ እናንተ ይምጣ” የሚል ሽሙጥ የጀመረች ትመስላለች፡፡
ቸርነት መኮንን ይባላል፤ ውሎውን ፒያሳ ካደረገ ረዘም ያለ ጊዜ እንዳስቆጠረ ይናገራል፡፡ ፒያሳ ያልሞላ ታክሲ እስኪሞላ ሰዎችን በመጥራት፣ ዕቃ በመሸከምና ሌሎች ስራዎችን እየሰራ ኑሮውን ሲገፋ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ከእለት ወደ እለት የአካባቢው መቆሸሽና መጥፎ ጠረን መባባስ ለስራም ሆነ ለጤና እክል እንደሆነባቸው ይናገራል - ለእሱና ለጓደኞቹ፡፡ እናም በመንገድ ላይ መሽናትና ለመከላከል መላ ዘየዱ፡፡
“ሃሳቡን ያመነጩት ታሪኩና ሙራድ የተባሉ ጓደኞቻችን ናቸው፤ ስምንት ሆነን እንሞክረው በሚል ተስማማን” ይላል ቸርነት፡፡ ከዚያም ሃሳቡን ይዘው ወደ ወረዳ አንድ ፅ/ቤት መሄዳቸውን ገልፆ፤ ህገ-ወጥ መኪና አጣቢዎች ለውሃ መቅጃ ይጠቀሙበት የነበረውንና  ቀበሌው በህገ-ወጥነት የወረሰውን የተወሰኑ ጀሪካኖች እንደሰጣቸው፣ እነሱም አዋጥተው ተጨማሪ ጀሪካን መግዛታቸውን ይናገራል፡፡
በአሁኑ ወቅት 15 ጀሪካኖችን ለአላፊ አግዳሚው በማቅረብ አካባቢው ላይ ሽንት እንዳይሸና መከላከል በመቻላቸው ከዚያ መጥፎ ጠረን እፎይታ መገኘቱን ቸርነት ገልጿል፡፡ በአካባቢው አራት ቦታ ላይ ሶስት ሶስት ጀሪካኖችን ደርድረው ያስቀምጣሉ፡፡ 25 ሊትር ውሃ የሚይዘው ጀሪካንም አንገት አንገቱ ተቆርጦና ክፍት ሆኖ ወገቡ ላይ በቀይ ቀለም “ሽንት መሽናት ይቻላል” የሚል ፅሁፍ ተፅፎበታል፡፡ ጀሪካኖቹ የተቀመጡበት የቆርቆሮ አጥር ላይ ደግሞ “እባካችሁ ጀሪካኑ ላይ በመሽናት ተባበሩን” የሚል ተማፅኖ አከል ማስታወቂያ ይታያል፡፡
“መቼም እንደ ስራ ከቆጠርነው አይቀር ብለን 50 ሳንቲምም አንድ ብርም ክፈሉ እንላለን፤ የሌለውን ግን አናስጨንቅም፤ ፍላጐታችን አካባቢው ንፁህ ሆኖ እኛም በሰላም ውለን እንድናመሽ ነው” የሚለው ወጣት ቸርነት፤ ሥራቸውን ሲያከናውኑ የሚያስፈራሯቸው፤ ማነህ ምንድነህ የሚሏቸው እንዲሁም ሊደበድቧቸው የሚጋበዙ፣ አንዳንዴም እላያቸው ላይ ሊሸኑ የሚቃጣቸው ሰዎች እንደሚያጋጥማቸው ይናገራል፡፡ “ይሁን እንጂ አላማ ይዘን እስከተነሳን ድረስ ሁሉንም በትእግስት እናልፋለን” የሚለው ወጣቱ፤ አንዳንድ ስልጣን አለን የሚሉ ግለሰቦችና ሊያግዙን የሚገባቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ሳይቀሩ ሥራችንን ያውኩብናል ብሏል፡፡
“በተቃራኒው ስራችንና ሞራላችን አስደስቷቸው 10 ብርም አምስት ብርም ሰጥተው አበረታተውን የሚሄዱ አሉ” ያለው ቸርነት፣ በዚህ ሁሉ መሃል መጠነኛ ለውጥ እያመጡ መሆናቸው እንደሚያስደስታቸው አጫውቶኛል፡፡ በአካባቢው አበባ በመትከል፣ ውሃ እየገዙና እየተሸከሙ በማጠጣት አካባቢውን ንፁህና አረንጓዴ ለማድረግ የጀመሩትን ጥረትም ወጣቱ አሳይቶኛል፡፡የክልል ከተሞች መንገድ ላይ ሶፍትና የማስቲካ ወረቀት መጣል አቁመው በዘመኑበት ወቅት የአፍሪካ መዲና የምትባለው ከተማ፤ እንዲህ መቆሸሿና የሚያቆሽሿትም በአብዛኛው አውቆ አጥፊዎች መሆናቸው እንደሚያሳዝነው ጠቅሶ፤ አንዳንዱ ሰው ጀሪካን ላይ ሸንቶ ክፈል ሲባል ለአንድ ብርና ለ50 ሳንቲም ደረሰኝ ሲጠይቀን ሳቃችን ይመጣል ብሏል፡፡
ስራውን እውቅና አግኝታችሁ ለመስራትና ራሳችሁን ከአንዳንድ ህገ-ወጦች ጥቃት ለመጠበቅ ለምን ከወረዳው ድጋፍ አትጠይቁም? በማለት ላነሳሁላቸው ጥያቄ ወጣቶቹ ሲመልሱ፤ በቀጣይ ተደራጅተው፣ የደንብ ልብስና መታወቂያ ኖሯቸው፣ ወረዳውም የዋጋ ተመን አውጥቶላቸው ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡
ወጣት ሃዱሽ ወርቅነህ በዚህ ስራ ላይ ከተሰማሩት ስምንቱ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ፒያሳን መዋያው ካደረገ ሰባት አመታት እንደተቆጠሩና ስራውን አምኖበት እንደሚሰራው፣ ሽናት ተሸክሞ በመድፋቱም የሚሰማው ነገር እንደሌለ ይናገራል፡፡ “በዋናነት የምንሰራው ስራ አለን፤ ከሰራን አይቀር ደግሞ ሳንቲም እናግኝ ብለን እንጂ ትኩረታችን አካባቢውን ማፅዳት ነው” ይላል፡፡ ስራው ፈተና ቢኖረውም ተስፋ በመቁረጥ ወደ ኋላ እንደማይሉ የገለፀው ወጣት ሃዲሽ፤ ጀሪካን ሙሉ ሽንት ተሸክሞ ቱቦ ውስጥ ሲደፋ የሚጠየፉት፣ የሚያላግጡበትና የሚያሽሟጥጡት ቢኖሩም እሱ ግን በስራውና በአካባቢው መፅዳት ከፍተኛ እርካታ እንደሚሰማው በልበ ሙሉነት ይናገራል፡፡
በቀን ምን ያህል ገቢ ታገኛላችሁ? ስል የጠየቅኩት ወጣት ሃዱሽ፤ “ገና ስራውን እንደጀመርን ጥሩ ገቢ ነበረን፤ ቢያንስ ዙሪያውን 12 ጀሪካን አስቀምጠን፣ በቀን እስከ 300 ብር ገቢ እናገኝ ነበር፤ አሁን አሁን ግን ሰው ከእኛ ጋር እየተላመደ ከሚከፍለው የማይከፍለው እየበዛ፤ ገቢው ቢቀንስም እኛ ግን አካባቢውን ለማፅዳት ያለን ቁርጠኝነት አልቀነሰም” ብሏል፡፡ ሽንቱን የምትደፉበት ቱቦ ሌላ ብክለት አይፈጥርም ወይ ስል ተጨማሪ ጥያቄ አነሳሁበት፡፡ ቱቦው ሰፊና በደንብ የሚያወርድ ከመሆኑም በላይ  ሽንቱ ከተደፋ በኋላ፣ ውሃ ስለሚለቀቅበት ለብክለት እንደማይጋለጥ ወጣቱ ያስረዳል፡፡
በአካባቢው የተከሏቸውን አበቦች ሲኮተኩት ያገኘሁት ሌላው የቡድኑ አባል ሙራድ፤ “ቀን ቀን መንገድ ላይ መሽናት ቀርቷል፤ ምክንያቱም በየቀኑ አንድ ሰው ተራ እየገባ ዙሪያውን ይጠብቃል” ብሏል፡፡
“መንገድ ላይ እሸናለሁ፤ አትሸናም” በሚል በተፈጠረ ሙግትም በአንድ ግለሰብ መፈንከቱን ሙራድ ነግሮኛል፡፡ ወጣቶቹ መጀመርያ ላይ ቀበሌው እንዳገዛቸው ባይክዱም ተገቢውን ትኩረት አልሰጠንም ይላሉ፡፡ እንደ ታክሲ ተራ አስከባሪ፣ የደንብ ልብስ፣ መታወቂያና ሌሎች መለያዎች ቢዘጋጅልን ጥሩ ነው፤ እያገዝን ያለነው እኮ መንግስትን ነው ይላሉ - ወጣቶቹ፡፡
ቀደም ሲል ተንቀሳቃሽ የወንዶች መጸዳጃ ቤት እንደነበረው የሚናገረው አንድ የአካባቢው ነጋዴ፣ እኔ ጋ 50 ሳንቲም ላለመክፈል ከጎኔ አጥር ስር የሚሸኑ መንገደኞች ነበሩ፤ በዚህ የተነሳ መረረኝና ዘጋሁት ብሏል፡፡ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ በሰጡት አስተያየት፤ “ወጣቶቹ እየሰሩ ያሉት ጊዜያዊ ስራ የሚያመጣው ጊዜያዊ መፍትሄ ነው፤ መንግስት ዘላቂ መፍትሄና የአመለካከት ለውጥ ላይ አተኩሮ መስራት አለበት” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጤና ጽ/ቤት  ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከተዋል ተብለን ወጣቶቹን በማገዝ፣ ዘላቂ መፍትሄ በማምጣትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ወደ ጽ/ቤቱ ብንመላለስም “ስብሰባ ላይ ናቸው” በሚል ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡ አንዳንድ ያነጋገርናቸው የጽ/ቤቱ ሰራተኞች ግን ጉዳዩ በቀጥታ አይመለከተንም ብለዋል፡፡ “ከተማዋ ከአፈጣጠሯ የታቀደ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት የላትም፤ በዚያ ላይ አካባቢው መጠጥ የሚዘወተርበትና የብዙ ቦታዎች መነሻና መድረሻ በመሆኑ ችግሩን ከፅ/ቤቱ አቅም በላይ አድርጎታል” ባይ ናቸው - የፅህፈት ቤቱ ሠራተኞች፡፡
እስከመቼ እንደሚዘልቅ መገመት ቢያዳግትም እስከ ጊዜውም ቢሆን የአካባቢው ንፅህና ጉዳይ በስምንቱ ወጣቶች ትከሻ ላይ ያረፈ ይመስላል፡፡ ገንዘብ የሌላቸው አገልግሎቱን ለማግኘት ክፈሉ እንደማይባሉ የሚናገሩት ወጣቶቹ፤ ነገር ግን ቢያንስ ህብረተሰቡ የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶና ጥረታችንን በቅንነት ተመልክቶ ጀሪካን ላይ ቢሸና፣ አንዳንድ ግለሰቦችም ሊተናኮሉን ባይሞክሩ እስካሁን ከታየው የላቀ ለውጥ ለማምጣት እንችላለን ብለዋል  - ወረዳው ከለላ እንዲሰጣቸው በመማፀን፡፡  


         በየቀኑ በአማካይ ወደ 300 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በአፋር በኩል በህገ-ወጥ መንገድ ከሃገር ለመውጣት ሲሞክሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ተገለፀ፡፡ ሰሞኑን 70 ኢትዮጵያውያን በህገወጥ መንገድ ከአገር ለመውጣት ሲሞክሩ የመን ባህር ዳርቻ ላይ ህይወታቸው ማለፉ ድንጋጤን ፈጥሯል፡፡
ከትናንት በስቲያ የክርስቲያን በጐ አድራጐት ማህበራት ጥምረት (CRDA) አስተባባሪነት በተዘጋጀ የአንድ ቀን ጉባኤ ላይ የአፋር ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ተወካይ አቶ መሃመድ አንበሳ እንዳመለከቱት፤ በየቀኑ በህገወጥ መንገድ ከአገር ለመውጣት የሚሞክሩ ወደ 300 የሚጠጉ ስደተኞች እየተያዙ ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋሉትን ስደተኞች ለመመገብና የሎጅስቲክ ድጋፍ ለማድረግ ፖሊስ መቸገሩን ተናግረዋል፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለእነዚህ ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አስተዳደር የፍትህ ፖሊሲ ፕላኒንግና አተገባበር ሚኒስትር ዴኤታና ከሳውዲ ተመላሾች አቀባበል ግብረ ኃይል አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ፤ የዜጎች ለስራና ለተለያዩ ጉዳዮች ከሃገር መውጣት በየትኛውም ሃገር ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት በህገ ወጥ መንገድ ከሃገር የሚወጡ  ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስ የሚቻለውን ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ስደትን ለመቀነስ የስራ እድል ፈጠራን ማስፋትና አመለካከትን መቀየር ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ባለፈው አመት ከሳኡዲ  አረቢያ የተመለሱትን ኢትዮጵያዊያን በማረጋጋት በኩል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥሩ የሰሩ ቢሆንም የውጪ ሃገር ተስፈኝነት አመለካከትን በመቀየርና ስደተኞችን በማቋቋም ረገድ የሚጠበቅባቸውን አላደረጉም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
መንግስት ህገ ወጥ ስደትን ለመቀነስ የተለያዩ ሰራዎችን እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ህጋዊ ጉዞን ለመጀመር የሚያስችለው ህግ የመጨረሻው ረቂቅ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በጉባኤው ላይ በቀረቡ ጥናቶች፤ በአሁን ሰአት የህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር በሰሜንና በደቡብ ወሎ እየቀነሰ ቢሆንም ከሰሜን ሸዋ አካባቢ ያለው ፍልሰት የመጨመር አዝማሚያ ይታይበታል ተብሏል፡፡ በመድረኩ ላይ የአለማቀፉ ሰራተኞች ድርጅት (ILO) ያስጠናው ጥናት የቀረበ ሲሆን በጥናቱም  በህጋዊ መንገድ ከሃገር ከሚወጡት ዜጎች ይልቅ በህገ ወጥ መንገድ የወጡት በእጥፍ እንደሚበልጡ ተመልክቷል፡፡ ባለፈው አመት ከሳውዲ አረቢያ ተባረው ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ 170ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን መካከል አሁንም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተመልሰው የመሄድ ፍላጎት እንዳላቸው አይኤልኦ ባስጠናው ጥናት ተጠቁሟል፡፡ አብዛኞቹ ተወላጆች በሀገሪቱ ሰርቶ መለወጥ የሚያስችል ነገር መኖሩን ቢያምኑም ከመንግስትና ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ ድጋፍ ይጠብቃሉ ተብሏል፡፡ ከሳውዲ ሲመለሱ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተገባላቸው ቃል ተስፈኛ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ በአሁን ሰዓት አብዛኛዎቹ ተመላሾች ስልጠና የተሰጣቸው ቢሆንም በስኬታማ የስራ መስክ ላይ የሚገኙት አነስተኛ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ከአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ የመጡት አቶ አደላሁ ፈንቴ፤ ከሳኡዲ አረቢያ ከተመለሱት ኢትዮጵያውን መካከል ወደ 43 ሺ 625 ገደማ የሚሆኑት የአማራ ክልል ተወላጆች መሆናቸውን ጠቁመው ከእነዚህ ውስጥ ስልጠና ወስደው ወደ ተለያዩ ስራዎች የገቡት ወደ 16 ሺህ ገደማ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ ክልሉ ካሰበው አንፃር ወደ ስራ የተሰማሩት ቁጥራቸው ዝቅተኛ መሆኑን የጠቆሙት ተወካዩ፤ በቀጣይ ወደ 40 ሺ የሚጠጉትን ለማሰልጠን እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡ አይኤልኦ ያስጠናው ጥናት፤ ወደ አረብ ሃገራት ለመጓዝ የሚሹ ዜጎች በተናጥል ለህገ ወጥ ደላሎች የሚያወጡትን ወጪም ይጠቅሳል፡፡ ከፍተኛ ወጪ የሚያወጡት ከትግራይ ክልል የሚጓዙት ሲሆን በነፍስ ወከፍ እስከ 22 ሺ ብር ገደማ ለመጓጓዣና ለደላላ ያወጣሉ፣ ከደቡብ አካባቢ የሚጓዙት ወደ 21 ሺ ብር፣ ከአማራ ክልል ወደ 19 ሺህ፣ ከኦሮሚያ ክልል የሚጓዙት ወደ 17 ሺህ ብር እንዲሁም ከአዲስ አበባ መነሻቸውን አድርገው የሚጓዙ ወደ 12 ሺህ ገደማ እንደሚያወጡ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጓዦች የገንዘብ ምንጫቸው ብድር ነው ይላል ጥናቱ፡፡ የተቀሩት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሃብት በመሸጥ የሚጓዙ መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ወደ አረብ ሃገራት ሲጓዙም የሚያጋጥማቸው ትልቁ ችግር የቋንቋ ችግር ሲሆን ከተጓዦቹ ከ70 በመቶ በላይ የዚህ ችግር ሰለባ ይሆናሉ ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ሰሞኑን በህገ ወጥ መንገድ ወደ የመን ሊገቡ ሲሉ ባህር ላይ ከሞቱት ኢትዮጵያውያን መካከል የሃያ አንዱ አስክሬን መገኘቱን ዴይሊ ሜል የዘገበ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአደጋው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል፡፡

Published in ዜና

ድብደባና እንግልት ተፈፅሞብናል ብለዋል
           ያልተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ብጥብጥና ሁከት ለማስነሳት ከህግ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ “የፓርቲዎች ትብብር” አመራርና አባላት ከትናንት በስቲያ ከእስር የተለቀቁ ሲሆን መንግሥት በበኩሉ፤ የግንቦቱን ምርጫ ለማስተጓጐል በህገወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡
የትብብሩ አመራርና አባላት ፍ/ቤት ቀርበው ፖሊስ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ እንደጠየቀባቸው የሚታወቅ ሲሆን ከቀጠሮው በፊት ከእስር እንደተለቀቁ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ሐሙስ  የተለቀቁት የፓርቲዎች አመራርና አባላት ከ80 በላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከእስር የተለቀቁት አብዛኞቹ የፓርቲው አባላት በደረሰባቸው ድብደባ ወገባቸው ላይ መጐዳታቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ከትናንት በስቲያ ምሽት በህክምና ተቋማት የአልትራሳውንድ ምርመራ እንደተደረገላቸውና በተለይ ሴቶቹ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን ጨምሮ 52 የሚደርሱ የትብብሩ አባል ፓርቲዎች አመራሮች መደብደባቸውን እንዳረጋገጡ አቶ ዮናታን ተናግረዋል፡፡ ግለሰቦቹ ሰኞ ዕለት ፍ/ቤት ሲቀርቡ መደብደባቸውን ለፍ/ቤት እንዳመለከቱ የጠቆሙት ሃላፊው፤ ፍ/ቤቱ ድብደባው ተገቢ አለመሆኑን አስታውቆ በተገቢው መንገድ ይያዙ የሚል ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የፓርቲዎቹ አመራሮች እስሩንና ድብደባውን በመቃወም የረሃብ አድማ አድርገው እንደነበርም ታውቋል፡፡
ቅዳሜ ረፋድ ላይ የሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት ከሚገኝበት እንደራሴ ሆቴል አካባቢ 150 ሜትር ያህል እንደወጡ፣ ከኋላም ከፊትም በደህንነት ኃይሎች ተከበው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፣ ሌሎቹም ከመስቀል አደባባይ አካባቢ ተይዘው መታሰራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
መንግስት ባለፈው አርብ ህዳር 26 ምሽት “የተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ የለም” የሚል መግለጫ በቴሉቪዥን ከሰጠ በኋላ እንዴት ከሰልፍ ልትወጡ ቻላችሁ? ስንል የጠየቅናቸው፣ ኃላፊው፤ የተሰጠው መግለጫ ህግን የጣሰ በመሆኑ ህግን ለማስከበር ነው የወጣነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫም፣ ህገ-ወጥ ሰልፍ ያደረጉ ጥቂት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ኮሚሽኑ በህገወጦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፀ ሲሆን ግለሰቦቹ ህገወጥ ሰልፍ ለማድረግ ከመሞከራቸውም በላይ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ትንኮሳ ፈፅመዋል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ህዳር 29 በአሶሳ ከተማ በተከበረው 9ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ መንግስታቸው የግንቦቱን ምርጫ ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ሻዕቢያና ተላላኪዎቹን እንዲሁም ህገ ወጥነትን የሚያጣቅሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ለማምከን አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ ትብብር የፈጠሩት ፓርቲዎች ሰማያዊ ፓርቲ፣ የመላ ኢትዮጵያውን አንድነት ድርጅት፣ የመላ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የሶዶ ጎርደና ህዝብ ዲሞክራሲዊ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ፣ የኦሞ ህዝቦች ኮንግረስና የጌዴኦ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ሲሆኑ ምርጫ ቦርድ ለትብብሩ ዕውቅና አልሰጠሁም ብሏል፡፡
 የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚል የአንድ ወር የተቃውሞ ፕሮግራም አውጥቶ በየሳምንቱ የተቃውሞ ስብሰባ ለማድረግ አቅዶ የነበረ ቢሆንም አንዱንም ለማሳካት እንዳልቻለ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

በጠራው አስቸኳይ ጉባኤ፤ የአባላት ቁጥር በህገ ደንቡ እንዲካተት አድርጓል

        አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ ትናንትና ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ፤ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ቁጥርን በህገ ደንቡ ያካተተ ሲሆን ሌሎች ህገ ደንቦችንም አሻሽሏል፡፡ ፓርቲው መጪውን ምርጫ አስመልክቶ ለጠቅላላ ጉባኤ አባላትና በመላ አገሪቱ ለሚገኙ የፓርቲው የአመራር አካላት ቀንና በማታ ሲሰጥ የቆየውን ስልጠና ዛሬ ያጠናቅቃል፡፡ ለጠቅላላ ጉባኤው ከተጠሩት 320 አባላት ውስጥ 250 ያህሉ በጉባኤው ተገኝተዋል፡፡ ካባለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው እንዲያስተካክል ያቀረበለት ዘጠኝ ጥያቄዎች እንደነበሩ ያስታወሱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃ፤ ከዘጠኙ ጥያቄዎች ስምንቱ መመለሳቸውንና የጠቅላላ ጉባኤ አባላትን ቁጥር አሳውቁ የሚለው ጥያቄ ቀርቶ እንደነበር ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ቁጥር 320 መሆኑን ፓርቲው ለቦርዱ አሳውቆ የነበረ ቢሆንም ቁጥሩን በተሻሻለው ህገ ደንብ ውስጥ አስገቡ የሚል ምላሽ ከቦርዱ እንደመጣላቸው አስታውሰው፣ ይህንኑ ለማድረግ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራቱን አቶ አስራት ተናግረዋል፡፡ “እግረ መንገዱን ጠቅላላ ጉባኤው ከተጠራ አይቀር አንዳንድ መሻሻል ያለባቸው ህገ ደንቦችም ተሻሽለዋል” ብለዋል፡፡
ፓርቲው ሊያከናውናቸው ካቀዳቸው ስራዎች ውስጥ የቀረው ከምርጫው አስቀድሞ ስለ ምርጫውና በምርጫው ወቅት መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮች ለጠቅላላ ጉባኤ አባላትና በመላ አገሪቱ ለሚገኙ የፓርቲው የአመራር አካላት ስልጠና መስጠት እንደነበር የገለፁት ኃላፊው፤ ስልጠናው ከሃሙስ ጀምሮ ከጠቅላላ ጉባኤው ጎን ለጎን ቀንና ማታ ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ማምሻውን እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡ ለስልጠናና ለጠቅላላ ጉባኤው የመጡት አባላት ቁጥር ከ500 በላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አስራት፤ ከ400 ሺህ ብር በላይ ወጪ እንደሚያስፈልግና ገንዘቡ ከውጭ ደጋፊዎችና ከአባላት የሚሰበሰብ እንጂ በእጅ የሌለ ገንዘብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  ስልጠናው በዋናነት ምን ላይ እንደሚያተኩር የጠየቅናቸው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ አንድነት በምርጫው እንደሚሳተፍ ቀደም ሲል ማሳወቁን አስታውሰው፤ ምርጫው በሚካሄድበት ወቅት ፓርቲው የራሱን ታዛቢዎች ለማስቀመጥ፣ የአንድነት ደጋፊዎች ለመምረጥ እንዲመዘገቡ፣ በወቅቱ የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ፣ በአግባቡ ድምፅ ቆጥሮ ለመረከብ የሚያስችሉትን ሁኔታዎች ለማመቻቸት እንዲችል የሚያደርጉ ስልጠናዎች  ለአመራሮቹ እንደተሰጠና ከስልጠናው እንደተመለሱ አመራሮቹ ህዝቡን የማንቃትና ስልጠና የመስጠት ሥራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
“አንድነት በምርጫ ለመሳተፍ የወሰነው በፖለቲካ ምህዳሩ የተገኘ አዲስ ነገር ኖሮ ሳይሆን ፓርቲያችን በራሱ ጥረት የኢህአዴግ ስርዓት በዘንድሮው ምርጫ እንዲያበቃ ለማድረግ ነው” ያሉት አቶ አስራት፤ በአሁኑ ሰዓት ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሳይሆን፣ አማራጭ ሚዲያዎች ሳይገኙና በመሰል አጣብቂኝ ውስጥ ታፍኖ የሚካሄድ ምርጫ መሆኑን ግን ፓርቲያቸው እንደሚያውቅ ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

         የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (መድረክ) በነገው እለት በአዲስ አበባ ለሚያከናውነው ሰላማዊ ሰልፍ ያዘጋጃቸውን መፈክሮች ይፋ ያደረገ ሲሆን በግንቦቱ አገራዊ ምርጫ ጠንካራ ቅስቀሳ ሊያካሂዱ ይችላሉ የተባሉ አባሎቶቼ እየታሰሩብኝ ነው ብሏል፡፡ ለነገው የመድረክ የተቃውሞ ሰልፍ ወደ 37 የሚጠጉ መፈክሮች የተዘጋጁ ሲሆን አብዛኞቹ በግንቦት ወር የሚደረገው ሃገራዊ ምርጫ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡
“የሃገራችን ችግሮች በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ በሚገለፅ የህዝብ ውሳኔ እንጂ በኃይል እርምጃ አይፈቱም”፣ “በማስመሰያ ምርጫ በየአምስት አመቱ ህዝብን ማታለልና ሀብቱን ማባከን ይቁም”፣ “የማስመሰያ ምርጫ ለማካሄድ ለሚባክነው የሃገርና የህዝብ ሃብት ኢህአዴግ ተጠያቂ ነው”፣ “ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ይቋቋም”፣ በመንግስት ሃብትና ንብረት ኢህአዴግ የሚያካሂደውን ህገ ወጥ የምርጫ ዘመቻ እናወግዛለን፡፡
” የሚሉት ይገኙበታል፡፡
መድረክ ስለ ህግ የበላይነት፣ ስለ ፍትሃዊ የሚዲ አጠቃቀም፣ ስለ መደራጀትና መሰብሰብ መብት፣ ስለ ማህበራዊ አገልግሎት ችግር የሚያትቱ መፈክሮችንም ያዘጋጀ ሲሆን ስለ ኑሮ ውድነት፣ ስለ ህገወጥ የመሬት ወረራ እንዲሁም የመንግስት በሃይማኖት ጣልቃ መግባትን የሚኮንኑ መፈክሮችንም እንዳዘጋጀ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልል በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በቀጣዩ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ ይኖራቸዋል ተብለው የተገመቱ አመራሮቹና አባሎቹ ለእስር እየተዳረጉበት መሆኑን መድረክ አስታውቋል፡፡

Published in ዜና

የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በነገው እለት በመቀሌ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
በመቀሌ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ በግንቦቱ ምርጫ በኑሮ ውድነት፣ በሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ የጠቆመው ፓርቲው፤ በስብሰባው ላይ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደን ጨምሮ በርካታ አመራሮች እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡ ፓርቲው በአዲስ አበባና በባህር ዳር በተከታታይ ሊያካሂዳቸው የነበሩ ህዝባዊ ስብሰባዎች እንደተሠናከሉበት ጠቁሞ ባለፈው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ካቀደቸው ስብሰባዎች አንደኛው ተሣክቶለት ህዳር 27 በሙሉአለም የባህል ማዕከል በአጥጋቢ ሁኔታ ማከናወኑን አስታውቋል፡፡
በስብሰባው ላይ 1500 የሚደርሱ አባላትና ደጋፊዎች የተሳተፉ ሲሆን በምርጫ፣ በሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እና በኑሮ ውድነት ዙሪያ ውይይት መካሄዱን ፓርቲው ጠቁሟል፡፡
ከዲሞክራሲያዊ መብቶች ዋነኛው የመሰብሰብ መብት ነው ያለው ፓርቲው፤ በቀጣይ በአዲስ አበባም ሆነ በተቀሩት የሃገሪቱ ክልል ከተሞች ተከታታይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል፡፡

Published in ዜና
Page 10 of 13