ሺ ጊዜ የሰማናቸው ተመሳሳይ “ጥንታዊ ዜማዎችን” እና እልፍ ጊዜ ያየናቸው ተመሳሳይ “ልማዳዊ ውዝዋዜዎችን” በቴሌቪዥን እየተጋትን የት እንደምንደርስ እንጃ። ያንገሸግሻል - አዳዲስ ፈጠራዎችን መስማትና ማየት ለሚፈልግ ሰው።
“ባህላዊ”፣ “አገራዊ”፣ “ብሄረሰባዊ” .... እያልን የተለያየ ስም ልንሰጣቸው እንችላለን። ግን፣ ስያሜ ስለተቀየረላቸው ብቻ፣ አዲስ ፈጠራ አይሆኑም። ያው ጥንታዊና ልማዳዊ ናቸው።
ተራው ሰው፣ ነሸጥ ሲያደርገው ለጨዋታና ለመግባቢያ፣ በየአጋጣሚውም ሰርግና ልደት ለመሳሰሉ ድግሶች ማድመቂያ፣ ጥንታዊዎቹን ዜማዎች ቢያንጎራጉር፣ ልማዳዊዎቹን ውዝዋዜዎች ቢጨፍር ተገቢ ነው። ሙያው አይደለማ። ሙያው ያልሆነ ሰው ደግሞ፣ ከጥንት የወረሰውን ዜማ ከማንጎራጎርና በልማድ የተረከበውን ውዝዋዜ ከመድገም ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም።
ለ“ኪነጥበብ ባለሙያ” ወይም ለ“አርቲስት” ግን፣ አይመጥናቸውም። እንደተራ ሰው ጥንታዊውን ዜማና ልማዳዊውን ውዝዋዜ እየኮረጁ መኖር፣ ከኪነጥበብ ሰው አይጠበቅም። የድሮ ፈጠራዎችን መኮረጅ፣ መደበኛ የዘወትር ስራቸው መሆን የለበትም። ሙያውን አሳንሶ ክብሩን እንደማሳጣት ነው የሚቆጠረው። ደግሞስ፣ የኪነጥበብ ሰዎች አዲስ ዜማና ውዝዋዜ ካልፈጠሩ፣ ማን ሊፈጥር ይችላል? አብዛኞቹኮ የኩረጃ ውድድር ውስጥ የገቡ ነው የሚመስሉት።
ለማጅ ድምፃዊያን፣ የሌላ ሰው ዜማ እየዘፈኑ ቢወዳደሩ አይገርምም። ጀማሪ የidol ተወዳዳሪዎች፣ በየተራ እየመጡ ቴዎድሮስ ታደሰ የተጫወታቸውን ዜማዎች እያንጎራጎሩ ይወዳደሩ የለ? ግን እድሜ ልክ እየኮረጁ ለመቀጠል አይደለም። ቀደምት የፈጠራ ሥራዎችን ከማድነቅ ተነስተው፣ ከዚያም ላይ ተምረውና ልምድ ቀስመው፣ ወደፊት የራሳቸው ጥበብ መፍጠር ይችሉ እንደሆነ ለማየት ነው የሚወዳደሩት። አርቲስት የመሆን ተስፋ እንዳላቸውና እንደሌላቸው ለማወቅ ነው፣ የሌላ ሰው ዜማ በመዝፈን የሚወዳደሩት። ገና አርቲስት ስላልሆኑ፣ አዲስ ፈጠራ ማቅረብ አይችሉማ።
ታዲያ፣ በምን ሂሳብ ነው፣ ጥንታዊ ዜማዎችንና ልማዳዊ ውዝዋዜዎችን እየኮረጁ ማቅረብ፣ የአንጋፋና የታዋቂ አርቲስቶች መደበኛ ስራ የሚሆነው? በኢቲቪ የሚቀርቡ አዳዲስ የሙዚቃ ክሊፖችኮ፣ በአብዛኛው የጥንታዊ ዜማና የልማዳዊ ውዝዋዜ ኩረጃዎች ናቸው። ቅድም እንዳልኩት፣ “ባህላዊ” ዜማ፣ “አገራዊ” ዘፈን፣ “የብሄር ብሄረሰብ” ጭፈራ... የሚሉ ስያሜዎች ሊያጣሉን አይገባም። ዋናው ቁምነገር፣ የጥንት አርቲስቶች ፈጠራ እንጂ፣ የዛሬ አርቲስቶች ፈጠራ አለመሆናቸው ነው።
በእርግጥ፣ አንዳንዴ ከጥንታዊው ዜማ በመነሳት፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያቀርቡ አርቲስቶች መኖራቸው አይካድም። ሙሉቀን፣ አስቴር አወቀ፣ ጌታቸው ካሳ፣ ስለሺ ደምሴ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል። ግን፣ ኢቲቪ “የባህል ዘፈን” ብሎ የሚያቀርብልን፣ የእነዚህ ድምፃዊያን ስራዎችን አይደለም።
“የባህል ዘፈን” የሚል “ክብር” በአብዛኛው ከጥንት ተኮርጆ የተሰራ መሆን አለበት። ኩረጃ ሲያስከብር ይታያችሁ። የጥንቱ ዜማ ብዙም አይቀየርም። ለነገሩ የዘፈኑ ግጥምም ከድሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መሆን አለበት። አለባበስና አጨፋፈርም እንዲሁ፣ በልማድ የተወረሰ መሆን ይኖርበታል። ጨዋታው ያለው ምን ላይ ነው? እንዲያው ለስሙ ሌጣ ኩረጃ እንዳይሆኑ፣ ላይ ላዩን መቀባባት፣ እዚህና እዚያ መከርከም፣ ከጫፍና ጫፍ ማበጠር ብቻ ነው። ከሳር ጎጆ ሳንላቀቅ፣ አንዴ ከሳሩ አናት ላይ የእንስራ ገል በማስቀመጥ፣ ሌላ ጊዜ የጎጆዋን ድንክዬ በር ወደ ደቡብ አቅጣጫ በማዞር፣ ወይም በዙሪያዋ ቅል በማንጠልጠል፣ “አዲስ የቤት አሰራር ፈጠራ አመጣሁ” ብሎ እንደመኩራት ቁጠሩት። እንዲህ እያልን፣ የእንስራ ስባሪውን የምናስቀምጥበትና ቅሉን የምናንጠለጥልበት ቦታ ማለቁ ይቀራል?  እስከ መቼ ያዛልቃል?
የጥንታዊዎቹ ዜማዎችና የልማዳዊ ውዝዋዜዎች ላይ የሚቀባው፣ የሚከረከመውና የሚበጠረው ነገርስ ተንጠፍጥፎ አያልቅም? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያለቀ የመጣ ቢመስልም፣ ልንለቃቸው ፈቃደኛ አይደለንም። ብዙ አርቲስቶች፣ በድሮው ላይ አንዳች የምትቀባ ነገር ለማግኘት መከራቸውን ያያሉ። ለአዲስ ፈጠራ ከመነሳሳት ይልቅ፣ ነባሩን አንጠፍጥፎና አሟጥጦ ለመጠቀም መሻማት ይሉሃል ይሄ ነው።
የአማርኛ፣ የትግርኛ፣ የኦሮሚኛ፣ የጉራጊኛና መሰል ጥንታዊ ዜማዎችና ልማዳዊ ውዝዋዜዎች ላይ፣ ከጎንና ጎን እየቆረጡ በመቀጠል፣ ከራስጌና ከግርጌ እየቀባቡ፣ እያፈጠኑና እያረገቡ፣ እያጯጯሁና እያርገበገቡ... ያቀረቡልንን የኩረጃ ስራ ለበርካታ አመታት አድምጠናል፤ ተመልክተናል። ኩረጃው ከመብዛቱና ከመደጋገሙ የተነሳ፣ ከእንግዲህ በእነዚህ ዜማዎችና ውዝዋዜዎች ዙሪያ፣ በቀላሉ ቀባብቶ የመኮረጅ እድል እየተሟጠጠ መጥቷል። ለዚህም ይመስላል፤ የባለፉት አምስት አመታት የደቡብ ክልል ጥንታዊ ዜማዎችና ልማዳዊ ውዝዋዜዎች ላይ ሰፊ ዘመቻ የተካሄደው። በእርግጥም፣ ለተወሰነ ጊዜ ትኩረትን የሚስቡ የኩረጃ ፈጠራዎችን ለማየት ችለናል። አሁን እንደምታዘበው ከሆነ ግን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ድግግሞሽ እየበረከተ፣ ስራዎቹ ለዛ እያጡ፣ ለቅምሻ ያህል እንኳ የፈጠራ ምልክት እየራቀቸው ነው። ቢሆንም፤ ኩረጃው መቀጠሉ አይቀርም - እንጠፍጥፎና አሟጥጦ ለመጠቀም!

በአረንጓዴ ቁምጣ ምትክ ሃምራዊ ቁምጣ
ትዝ ይላችሁ እንደሆነ፣ ከጥቂት አመታት በፊት በሚቀርቡ የአማርኛ “ባህላዊ” ጨዋታዎች ላይ፣ የወንድ ተወዛዋዦች ልብስ በአብዛኛው የሸማ ወይም የአቡጀዲ ልብስ ነበር - ጥብቆ፣ ተነፋነፍ፣ እጀ ጠበባ ወዘተ...። አሁን ያ በሌላ ተቀይሯል። በቲሸርትና በሱሪ፣ በሸሚዝና በቁምጣ... አንዳንዴም በጂንስ ሆኗል። ከዚህም ጋር ነው፣ የገጠር ሰዎችን ውዝዋዜ ቀርፆ የማሳየት ፈሊጥ ብቅ ያለው። ውዝዋዜው ሳይቀየር፣ አለባበስና የተወዛዋዦቹ ማንነት ስለተለወጠ ብቻ፣ እንደ አዲስ ፈጠራ ነበር የታዩት። ከጀማሪዎቹ መካከልም “ባላገሩ” በሚል ስያሜ የቀረቡ ክሊፖች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ይመስለኛል። በእርግጥም፤ ያኔ ስናያቸው የነበሩ የሸማ አለባበሶች፣ ገጠር ውስጥ ተረት ሆነው የቀሩት ገና ድሮ ነው። የ“ባላገሩ” ክሊፖች፣ የገጠር አለባበስ እንደተቀየረ የገባቸው ይመስላል። የገጠር ነዋሪዎች ጭፈራ ማካተቱም፣ ነገሩን በደንብ እንድናየውና ጥያቄ እንድናነሳ እድል ይሰጣል። ለምን በሉ።
የገጠር ጎረምሳና ኮረዳ አሳምረው የሚወዛወዙ ከሆነ፣ የነሱን ኮርጆ የሚወዛወዝ ከተሜ ለምን “አርቲስት” ወይም “የኪነጥበብ ባለሙያ” የሚል ማዕረግ ይሰጠዋል? በእርግጥ የገጠሮቹ ወጣቶችም፣ ከአባት ከእናት ኮርጀው ነው። ነገር ግን፣ የገጠሮቹ ወጣቶች በሙያ ገበሬዎች ናቸው። አርቲስት ነን አይሉም። ታዲያ፣ ጥንታዊውን ውዝዋዜ ከወላጆቻቸው የኮረጁ የገጠር ወጣቶች፣ “ተወዛዋዥ አርቲስት ወይም የዳንስ ባለሙያ” ካልሆኑ፣ ውዝዋዜያቸውም እንደ ፈጠራ የማይታይ ከሆነ፣ እንዴት ነው የኩረጃ ኩረጃ እንደ ፈጠራ ስራ የሚቀርብልን - ለዚያውም በውዝዋዜ አርቲስቶች፣ በፕሮፌሽናሎች።
እውነት ለመናገር፣ የገጠር ገበሬ ውዝዋዜና የከተሜ አርቲስት ውዝዋዜ “በአቀራረብ” ይለያል። አርቲስቶች ያመጡት ለውጥ ምን መሰላችሁ? አንደኛውና ደምቆ የሚታየው ልዩነት፣ የልብስ ቀለም ነው። ከገጠር ወጣቶች በተለየ ሁኔታ፣ ፕሮፌሽናል ተወዛዋዦች አለባበስ የተዘበራረቀ አይደለም። እንደዩኒፎርም ነው ልብስ አሰፍተው የሚለብሱት - “ባህላዊ ልብስ” መሆኑ ነው።
እንዲያም ሆኖ “ባህላዊ” ወይም “ልማዳዊ” የሚባሉ የልብስ አይነቶችን በሙሉ አይተን የጨረስን ይመስለኛል። “አዲስ ፈጠራ” የምናይ ከሆነ ከልብስ የቀለም ለውጥ አያልፍም። አረንጓዴ የነበረው የተወዛዋዦች ቁምጣ፣ በሌላ ዘፈን በሃምራዊ ቀለም የደመቀ ቁምጣ ሆኖ ይመጣል። በዛጎል ጥለት የተሸፈነ ጉርድ ሸሚዝ ውልቆ፣ በረድፍና በመስመር የልብስ ቁልፎችን የተዥጎረጎረ ጉርድ ሸሚዝ ይለበሳል። በባለ ቢጫ ሸንተረሩ ሰማያዊ ቲሸርት ምትክ፣ ቀይ ሸንተረሮች የተጋደሙበት አረንጓዴ ቲሸርት ተተክቷል። በ“ባህላዊ” የዘፈን ክሊፖች ላይ የምናየው “አዳዲስ ፈጠራ”፣ ከጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችና ከልብስ ሰፊዎች የቀለም ግዢ ብዙም አይለይም።
በአጠቃላይ፣ “ባህላዊውን እስክስታ”፣ “አገራዊውን ውዝዋዜ” ወይም “የየብሄረሰቡን ጭፈራ”…  በአብዛኛው ከየአይነቱ እልፍ ጊዜ በተደጋጋሚ ብናይም፤ “ይብቃችሁ” የሚል አላገኘንም። ያንኑ ተመሳሳይ እስክስታ በሌሎች ተወዛዋዦች፣ ተመሳሳይ ውዝዋዜ ከሌላ ዘፋኝ ጋር፣ ተመሳሳይ ጭፈራ በሌላ ጊዜ እየተደጋገመ መምጣቱ አላቆመም። “ተመሳሳይ ቢሆንም አዳዲስ ነገሮችን ይዘው የሚመጡም ይታያሉ” የሚል ሰው ካለ አልተሳሳተም።
እጃቸውን ወገባቸው ላይ አሳርፈው፣ ወይም ዱላ ጨብጠው፣ አልያም የመቀነት ጫፍ ይዘው ሲወዛወዙ የነበሩ ባለሙያዎች፣ በሌላ ዘፈን እጃቸውን የቁምጣ ኪሳቸው ውስጥ አስገብተው ያንኑን ተመሳሳይ ውዝዋዜ ይደግሙታል። አልፎ አልፎ፣ ጉልበት ጨምረውበት ሲወዛወዙ አቅርቦ የሚያሳይ ቀረፃም ይመጣል። ጉልበት እየጨመሩ፣ ውዝዋዜውን ወደ መንገጫገጭና መንፈራገጥ እያመዘነ መሄዱ፣ “ጥሩ ፈጠራ ነው” ያስብለዋል ብዬ ግን አላምንም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሴት ተወዛዋዦች ይልቅ ወንድ ተወዛዋዦች እየበረከቱ የመጡትም በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
አሁን አሁንማ፣ እጅ ኪስ ውስጥ አስገብቶ ወይም በጉልበት እየተወራጩ መወዛወዝን የመሳሰሉ “ፈጠራዎችም”ቀስ በቀስ እየተሟጠጡ ሳይሆኑ አይቀርም። የተወዛዋዦቹን ቁጥር ማብዛትና ማሳነስምኮ ራሱን የቻለ አዲስ ፈጠራ ነው ካላልን በቀር ማለቴ ነው። ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሁለት የተለመዱ የውዝዋዜ አይነቶችን አቀላቅሎ ማቅረብስ አዲስ ፈጠራ ነው? መሞከር አይከፋም። ግን፣ በአንዳች ዘዴ ሁለቱን ልማዳዊ ውዝዋዜዎች አዋህዶ ወይም አቀናብሮ፣ አንዳች አዲስ ትዕይንት ካልፈጠረ በቀር፣ ሺ ጊዜ በየተራ ያየናቸውን ጥንታዊ ውዝዋዜዎች ማዶ ለማዶ አስቀምጦ ቢያፈራርቅብን ምን ዋጋ አለው? እሺ ዋጋ ይኑረው። ለ1001ኛ ጊዜ ውዝዋዜዎቹን ማየት፣ የራሱ የሆነ ዋጋ ይኖረዋል እንበል። ነገር ግን አዲስ ፈጠራ ነው ተብሎ፣ እውቅና የሚጠየቅበት ሊሆን ይችላል?     
ከእለት ተእለት ብቻ ሳይሆን፣ ከአመት አመት የጥንት ዜማዎችን መስማት፣ ልማዳዊውን ጭፈራ የሚያስነኩ ተወዛዋዦችን ማየት አይሰለችም? ከአመት አመት የማይቀየር ነገር ማየት፣ ከማሰልቸትም አልፎ የመታፈን ስሜትንም ሊፈጥር ይችላል። አገሪቱ፣ አንዳች የጊዜ ስንጥቅጥ ውስጥ ተቀርቅራ፣ በህልም ሩጫ ውስጥ ያለመፈናፈኛ፣ እንደ ነባሩ ጭፈራ ባለችበት ቦታ  እየረገጠችና እየተንፈራገጠች የምትባክን አትመስልም? ለዚያውም፣ በተመሳሳይ አለባበስ (አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጎን ተሰልፈው)፣ ለዚያውም በተመሳሳይ ቦታ (አብዛኛውን ጊዜ ገጠር ውስጥ አረም በወረረው ቦታና ከሳር ጎጆ አጠገብ) ነው ዘፈኖቹና ውዝዋዜዎቹ የሚቀርቡት። እንዲያው ስታስቡት፣ በዛሬው ዘመን የገጠር ኑሮን ማሞካሸትና የሳር ጎጆን ማሞገስ ምን ያደርግልናል?

የሳር ጎጆንና ሽሮን የመናፈቅ ወግ
የገጠር ወጣቶችኮ፣ ኑሮ እያማረራቸው ነው ወደ ከተማ የሚጎርፉት። ወደ ገጠር የሚፈልስ የከተማ ወጣትስ አለ? የለም። ታዲያ ለምንድነው ከተሜ ኢትዮጵያውያን ገጠርን የሚያሞካሹት? ገጠር ሄደው መኖር አይፈልጉም። ወደ ገጠር ከሄዱም፣ የሙዚቃ ክሊፕ ቀርፀው ለመመለስ ነው።
ገጠሬው በዚህም ብሎ በዚያ፣ ከብትና ሰው ተፋፍጎ የሚያድርባትን የሳር ጎጆ፣ በባለ መስኮት ክፍሎች ለመቀየር፣ የሳር ጣራውን በቆርቆሮ ለመቀየር ደፋ ቀና ይላል።
ወገኞቹ ከተሜዎችስ? ከተማ ውስጥ የሳር ጎጆ አስመስለው ለመስራት ይሞክራሉ። ወይም ደግሞ፣ የሳር ጎጆ አጠገብ በአረም የተወረረ ቦታ ላይ ይዛወዛሉ። “እንደ ሽሮ የምወደው ምግብ የለም” ብሎ ከሚናገር ወገኛ ዳያስፖራ ምንም ልዩነት የለውም።
የድሮ ዘፋኞች፣ የህንፃ ጣሪያ ላይ፣ ቪላና ሳሎን ቤት  ወይም መናፈሻ ውስጥ ብቻ ነው ክሊፕ የሚሰሩት እየተባሉ ሲተቹ ትዝ ይለኛል። እና አሁን፣ የሳር ጎጆ አጠገብ መወዘወዝና በአረም የተወረረውን ማሳ እየረገጡ መጨፈር ይሻላል? ብዙ ክሊፖች ላይ የምናየው ይሄው ነው። አለበለዚያ ደግሞ፣ አስፋልት መሃል ላይ ሲወዛወዙና ሲዘፍኑ። አስፋልት መሃል፤ ከመኪና ጋር እየተጋፉ! በየቀኑ ስለመኪና አደጋ የሚለፈልፉት እነ ሳጅን፣ አደጋውን ለመቀነስ አለመቻላቸውና ድካማቸው ከንቱ መሆኑ ምኑ ይገርማል?

ማንነትና ፈጠራ የነጠፈበት ኋላቀር ባህል
በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላ ወገኛ መከራከሪያ መቅረቡ አይቀርም። “የባህል ዘፈኖቻችን” እና “የብሄረሰብ ጭፈራዎቻችን”፣ “ቋንቋዎቻችን”... የማንነታችን መገለጫ ናቸው፤ ከእነሱ ውጭ ማንነትና ህልውና የለንም... ብሎ የሚከራከር ሰው አይጠፋም። ወገኛ በሉት። የገጠርወጣቶች ህይወታቸውን ለማሻሻል ወደ ውጭ አገራት የሚሰደዱት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የከተማ ወጣቶች ዲቪ የሚሞሉት ለምን ይመስላችኋል? አማርኛ ወይም ትግርኛ፣ ኦሮሚኛ ወይም ጉራጊኛ፣ ሱማሊኛ ወይም ሲዳምኛ፣ አፋርኛ ወይም ወላይትኛ ፈለጋ ነው አሜሪካ ለመሄድ መቶ ሺ ብር የሚከፍሉት? ጥንታዊ ዜማና ልማዳዊ ጭፈራ ለማግኘትና በባህርና በበረሃ ወደ አረብ አገራት የሚሰደዱት? የኑሮ መተዳደሪያ ለማግኘትና በዚህም፣ ህልውናቸውን ለመጠበቅና ማንነታቸውን ለመገንባት ነው።
ለነገሩ፣ ጥንታዊ ዜማና ልማዳዊ ውዝዋዜ ላይ ሙጭጭ ብሎ ኩረጃን እንደጣኦት ማምለክ፣ አገርንና ባህልን ማክበር ሳይሆን፣ መናቅ ነው። አዲስ ፈጠራ የማያፈልቅ አገርና ባህል ምኑ ይከበራል?
መቼም እነዚያ ጥንታዊ ዜማዎችና ውዝዋዜዎች ከእነ ሉሲ ጋር አብረው የተፈጠሩ አይደሉም። ከምድር የበቀሉ ወይም ከሰማይ የወረዱም አይደሉም። የሆኑ ምርጥ የፈጠራ ሰዎች፣ የሆኑ ኢትዮጵያውን ድንቅ ጥበበኞች ናቸው ዜማዎቹንና ውዝዋዜዎቹን የፈጠሯቸው።
ከነሱ በፊትም ዜማና ውዝዋዜ እንደነበረ አያጠራጥርም። ግን የድሮውን በመኮረጅ እዚያው እየረገጡ እድሜያቸውን የሚጨርሱ አይነት ደካማ ሰዎች አልነበሩም ማለት ነው። አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያፈልቅ የተከበረ አገርና ባህል ነበራቸው ማለት ነው። ያንን ክቡር ባህልና አገር መጠበቅ የሚፈልግ ሰው፣ የድሮዎቹን ፈጠራዎች እያደነቁ እንደነሱ በተራው አዳዲስ የጥበብ ፈጠራዎችን ያመነጫል። ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ የሚያመነጩ ፈጣሪዎችን ያበረታታል። ካልሆነም የፈጠራ ስራዎችን ለማየት ይመኛል።  
እንዴት መሰላችሁ? ሰውን ከዋሻ ኑሮ ያላቀቀ የሳር ጎጆ፣ በአፈታሪክ ብቻ ከመምታታት ሊገላግል የሚችል የብራና ላይ ፅሁፍ፣ አፈር ላይ ከመንከባለል የሚያድን ባለሶስት እግር በርጩማ... እነዚህ ሁሉ የጥንት ዘመን ምርጥና ድንቅ ፈጠራዎች ናቸው። ጎጆ፣ ብራና ወይም በርጩማ ላይ ሙጭጭ ብለን ከቀረን፣ ጥንታዊዎቹን የፈጠራ ሰዎችና ባህላቸውን እንደማዋረድ ነው የሚቆጠረው። እንደነሱ አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያፈልቅ ባህልና አገር የለንም ማለት ነው።
የጥንት አባቶቻችን ባህል፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያፈልቅ የስልጣኔ ባህል ሲሆን፣ የኛ ባህል ግን ከኩረጃ ባሻገር መመልከት የተሳነውና ፈጠራ የነጠፈበት ኋላቀር ባህል ሆኗል።   
ነገሩ ሌላ ተጨማሪ ገፅታም አለው። በዜማና በውዝዋዜ ጥበብ ላይ ለፈጠራ መሟጠጥ ትልቁ መንስኤ፣ የኋላቀርነት ባህል ቢሆንም፣ ኢቲቪም ትልቅ ድርሻ አለው። አንድም “አገራዊና ልማታዊ” አልያም “ባህላዊና ብሄረሰባዊ” የሙዚቃ ክሊፖችን ነው በብዛት የሚያስተናግደው። አማራጭ ያጣ አርቲስት ሁሉ፣ ኢቲቪን ለማስደሰት “ጥንታዊ ዜማ”ና “ልማዳዊ ውዝዋዜ” ላይ ቢረባረብ አይገርምም። 

በተሰማሩበት መስክ ጉልህ ስራ ሰርተዋል፣ የላቀ ውጤት አስመዝግበዋል፣ ብዙዎችን ተጠቃሚ አድርገዋል፣ ሃያልነታቸውንም አስመስክረዋል ያላቸውን የአለማችን ሴቶች በየአመቱ የሚመርጠው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ ዘንድሮም የ2013ን የአለማችን 100 ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
ፎርብስ በመላ አለም ከሚገኙ የተለያዩ አገራት ከመረጣቸው 100 የአመቱ ሃያላን ሴቶች መካከል፣ የቀለም ልዩነት ሳይበግራቸው ጉልህ ስራ ሰርተዋል፣ የጥቁር ሴቶች የስኬታማነት ተምሳሌት ሆነዋል ብሎ በዝርዝሩ ውስጥ ያካተታቸው ጥቁር ሴቶች አስራ አንድ ብቻ ናቸው፡፡ ከአስራ አንዱ ጥቁር ሃያላን ሴቶች መካከልም፣ ከአፍሪካ አህጉር የተመረጡት ሶስት ብቻ ናቸው፡፡
ፖለቲከኞችን፣ የኩባንያ ስራ አስኪያጆችን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሃላፊዎችን፣ የመንግስት ባለስልጣናትንና በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ሴቶችን የያዘው የፎርብስ የአመቱ ምርጥ ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ከጥቁር ሴቶች መካከል በቀዳሚነት ያስቀመጠው ቀዳማዊ እመቤት ሚሼል ኦባማን ነው፡፡
ፎርብስ ሚሼል ኦባማን የመረጠው፣ በቀዳማዊ እመቤትነቷ በመጠቀም ህጻናትን ከመጠን በላይ ከሆነ ክብደት ለመታደግና ጤናማ አኗኗርና አመጋገብን ለማስፋፋት በምታደርገው ጥረት ነው፡፡ ሚሼል ከባራክ ኦባማ ጋር ሲነጻጸር በአሜሪካውያን ዘንድ የበለጠ ተወዳጅነት እንዳላቸው የገለጸው የፎርብስ መረጃ፣ ከአጠቃላዩ የአሜሪካ ህዝብ 67 በመቶ የሚሆነው ከባራክ ኦባማ ይልቅ ለሚሼል ጥሩ አመለካከት እንዳለው ያሳያል፡፡
በሃያላኑ ጥቁር ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተችው ሌላዋ አፍሪካ አሜሪካዊት ደግሞ ኦፕራ ዊንፍሬይ ናት፡፡ ለ25 አመታት ስትመራው በነበረው ኦፕራ ሾው የተባለ ፕሮግራም አለማቀፍ ዝናን ያተረፈችው ኦፕራ፣ በሃብት መጠን ቀዳሚዋ አፍሪካ አሜሪካዊት መሆኗንም ፎርብስ ጠቅሷል፡፡ አዲስ ያቀዋቀዋመችው ዘ ኦፕራ ዊንፍሬይ ኔትዎርክ የተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለፈው አመት ብቻ 83 ሚሊዮን ተመዝጋቢ ተመልካች ቤተሰቦችን ለማግኘት በቅቷል። ኦፕራ በበጎ አድራጎት ስራ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠራ የአለማችን ለጋስ ሴቶች አንዷ ስትሆን፣ እስከ አሁን ድረስ ከ400 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ስራ አበርክታለች፡፡
የዜሮክስ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነችው አሜሪካዊቷ ኡርሱላ በርንስ፣ ኩባንያውን ከማተሚያ መሳሪያ አምራችነት፣ ጠቅላላ አገልግሎቶችን ወደሚሰጥ ግዙፍ ኩባንያነት አሳድጋለች በሚል ነው በሃያላኑ ዝርዝር ውስጥ የተካተተችው፡፡ እ.ኤ.አ በ1980 በተለማማጅ ሰራተኛነት ዜሮክስ ኩባንያን የተቀላቀለችው ኡርሱላ በርንስ፣ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪዋን መመረቋን ተከትሎ በቀጣዩ አመት የኩባንያው መደበኛ ሰራተኛ ሆና ተቀጥራለች። በስራዋ ውጤታማ በመሆኗ እ.ኤ.አ በ2000 የኩባንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ተደርጋ ተሹማለች፡፡ ይህቺው ታታሪ ሰራተኛ እ.ኤ.አ በ2009 የዜሮክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከሆነች በኋላም፣ የበለጠ ውጤታማ ስራ በማከናወኗና ኩባንያውን ወደተሻለ ትርፋማነት በማሸጋገሯ ነው፣ ፎርብስ ከሃያላኑ ጎራ የቀላቀላት፡፡
ሌላዋ የፎርብስ የአመቱ ሀያል ሴት አሜሪካዊቷ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ ናት፡፡ ፎርብስ እንዳለው፣ ቢዮንሴ በሙዚቃ ስራዎቿ ከምታገኘው በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ በተጨማሪ፣ ሀውስ ኦፍ ዴሪዮን በሚል ስያሜ ባቋቋመችው የአልባሳት አምራች ኩባንያዋም ከፍተኛ ትርፍ ማካበቷን ቀጥላለች፡፡
ከፔፕሲ ጋር የፈጸመችው የማስታወቂያና የኮንሰርት ስምምነት 50 ሚሊዮን ዶላር ያሳፈሳት ቢዮንሴ፣ የምንጊዜም ምርጥ ሽያጭ ካስመዘገቡ የአለማችን ታዋቂ ድምጻውያን ተርታ የምትመደብ ሲሆን 17 የግራሚ ሽልማቶችንም ተቀብላለች፡፡ ከወራት በፊት በተዘጋጀ የሱፐር ቦውል የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ያቀረበችው የ15 ደቂቃ ሙዚቃዋን በአለም ዙሪያ የሚገኙ ከ104 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች እንደተመለከቱት የሚጠቅሰው የፎርብስ መረጃ፣ ድምጻዊቷ በአለም ዙሪያ ያላትን ተቀባይነት የበለጠ እያሳደገች መምጣቷ በሃያልነት እንዳስመረጣት ይናገራል፡፡
የታዋቂው ዎልማርት ኩባንያና ከአሜሪካ ታላላቅ የንግድ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው የሳምስ ክለብ ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን የሰራችው ሮዛሊንድ ብሪዌርም ሌላዋ የፎርብስ የአመቱ ሀያል ጥቁር ሴት ናት፡፡ ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ የሳምስ መሪ ሆና የተመረጠችው ብሪዌር፣ ለኩባንያው ትርፋማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷ ይነገራል። እ.ኤ.አ በ2006 ዎልማርትን በመቀላቀል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆና ያከናወነቻቸው ስራዎቿ ኩባንያውን ማሳደግ፣ የእሷን ጥንካሬም ማስመስከር የቻሉ በመሆናቸው በሃያላኑ ዝርዝር ውስጥ መካተቷን ፎርብስ ተናግሯል፡፡
አፍሪካን የጥቁር ሃያላን ሴቶች እናት አድርገው ካስጠቀሷት ሶስት የአመቱ የፎርብስ ሃያላን ሴቶች መካከል፣ የማላዊ ፕሬዚዳንት ጆይስ ባንዳ አንዷ ናት። የአገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት በመሆን ወደ መሪነት የመጣችው ጆይስ ባንዳ፣ የመጀመሪያዎቹን የስልጣን አመታት ከአለማቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ በማሰባሰብና አገሪቱን ከሚፈታተናት የዋጋ ግሽበት ጋር በመታገል ነበር ያሳለፈቻቸው፡፡
ጆይስ ባንዳ ከአጠቃላይ አመታዊ ገቢዋ 40 በመቶ ያህሉን ከውጭ እርዳታ የምታገኘውን ይህቺን ድሃ አፍሪካዊት ሀገር ከገንዘብ ዕጦት ለመታደግ፣ በአለም ዙሪያ እየተንቀሳቀሰች የገንዘብ ተቋማትን በማሳመን ስራ ተጠምዳ እንደኖረች ፎርብስ ተናግሯል፡፡ ባንዳ ያለፉት መንግስታት አያደርጉ አድርገዋት የሄዷትን ማላዊ እንድታገግምና ራሷን ችላ እንድትቆም ለማስቻል እያደረገችው የምትገኘው ተጠቃሽ ጥረት የፎርብስን ሚዛን በመድፋቱ ከሃያላኑ ጎራ ተቀላቅላለች፡፡
የአፍሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንትና እ.ኤ.አ የ2011 የኖቬል የሰላም ተሸላሚዋ ሊይቤሪያ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ የአፍሪካን ሴቶች ሃያልነት ያስመሰከረች ሌላኛዋ የፎርብስ ምርጥ ናት። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርቷን የተከታተለችው ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ የላይቤሪያን የእርስ በርስ ግጭት በሰላማዊ ድርድርና መግባባት ለመቋጨት ከመቻሏ በተጨማሪ፣ አለማቀፍ አበዳሪዎች የዕዳ ስረዛ እንዲያደርጉ በማግባባት ረገድ የሰራቻቸው ስራዎችም ጠንካራና ስኬታማ ሴትነቷን ያስመሰክራሉ ብሏል ፎርብስ፡፡
ፎርብስ የአመቱ ሃያል ሴት ብሎ የጠቀሳት ሌላዋ አፍሪካዊት፣ የናይጀሪያ የፋይናንስ ሚንስትርና የኢኮኖሚ አስተባባሪ ሚንስትር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ ናት፡፡ ኢዌላ በአለም ባንክ የነበራትን የማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ስራ ለቅቃ፣ እ.ኤ.አ ከ2011 በሚንስትርነት ከተሸመች በኋላ ተጠቃሽ ስራ መስራቷን የጠቀሰው የፎርብስ መረጃ፣ በቀጣዩ አመት የአገሪቱ ኢኮኖሚ 6.5 በመቶ እድገት እንዲያሳይ የእሷ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2003 እስከ 2006 በአገሯ ናይጀሪያ የኢኮኖሚ አማካሪ ሆና ትሰራ የነበረው ኢዌላ፣ አበዳሪዎች የናይጀሪያን 18 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ እንዲሰርዙ በማስቻል ረገድ ተጠቃሽ ስራ መስራቷ ይነገራል፡፡
ከፎርብስ የአመቱ ሃያላን ጥቁር ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተችዋ ሌላኛዋ ትጉህ ደግሞ፣ እ.ኤ.አ በ2012 የአለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሆና የተመረጠችው አሜሪካዊቷ ኤርታሪን ኮሲን ናት።
ድርጅቱ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 78 የተለያዩ አገራት ከርሃብ፣ የምግብ ዋስትናና የምግብ እጥረት ጋር  በተያያዘ የሚሰራውን ሰፊ ስራ በአግባቡ የመምራትና በስሯ የሚገኙ ከ15ሺህ በላይ ሰራተኞችን በወጉ የማስተዳደር ታላቅ ሃላፊነት የተጣለባት ኮሲን፣ ውጤታማ ስራ ማከናወኗን ፎርብስ ይመሰክራል፡፡ የመጀመሪያውን አመት በምዕራብ አፍሪካ በድርቅ፣ በሶሪያ ደግሞ በእርስበርስ ጦርነት ሳቢያ የተከሰተውን ርሃብ ለማሰወገድ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ያሳለፈችው ኮሲን፣ በቀጣይም ከምግብ እርዳታ ወደ ራስን ማስቻል የሚደረገውን ሽግግር በመምራት ተጠቃሽ ስራ ማከናወኗን ፎርብስ ዘግቧል፡፡
በሃያላኑ ዝርዝር ውስጥ ለመቀላቀል የቻለችው ሌላዋ አሜሪካዊት፣ የኬር ዩኤስኤ ፕሬዚደንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሄለን ጋይሌ ናት፡፡ እ.ኤ.አ በ2006  የኬር ዩኤስኤ ፕሬዚደንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆና የተሸመችው ሄለን፣ በ87 የአለም አገራት ድህነትን ለመዋጋት የሚከናወኑ ስራዎችን በአግባቡ መምራቷ ይነገርላታል፡፡
በቻድ፣ ኒጀር፣ ማላዊና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከ750 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ፣ የምግብና የንጹህ የውሃ መጠጥ አቅርቦት ስራዎችን አከናውናለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2003 ሮበርት ውድ ጆንሰን ፋውንዴሽን የተባለው የአሜሪካ ትልቁ የጤና ክብካቤ ተቋም ፕሬዚደንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆና የተመረጠችው ሪዛ ላቪዞ ሙርኒ፣ ሌላኛዋ የፎርብስ የአመቱ ሃያል ጥቁር ሴት ናት፡፡ ፋውንዴሽኑን ለአመታት በስኬታማነት መምራቷ የሚነገርላት ሙርኒ፣ ተቋሙን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት እንዲሁም የመጀመሪያዋ አፍሪካ አሜሪካዊ ናት፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የአዳማ ገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የህግ ማስከበር ሃላፊ የነበረው አቶ ተመስገን ጉላን በራሱና በወንድሙ ስም ከገቢው ጋር የማይመጣጠን ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ እና ንብረት ይዞ በመገኘቱ ክስ የቀረበበት ሲሆን በፖሊስ ክትትል ስር የነበረው ወንድሙም ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤት ቀርቦ ክሱ ተነቦለታል፡፡ ቀደም ሲል ተከሳሹ ሁለት ዶዘሮችን በ15ሚ.ብር መግዛቱን ደርሼበታለሁሲል አቃቤህግ መግለጫ መስጠቱ ይታወሣል፡፡
የ33 ዓመቱ የህግ ማስከበር ሃላፊ አቶ ተመስጌን ጉላን ዓለሙ፣ በሌላ ስሙ ተመስገን ስዩም አሰፋ፤ ሁለት ክሶች የቀረቡበት ሲሆን በግብረአበርነት በተያዙት የወልደሚካኤል ሃለፎም አጠቃላይ አስመጪና የፈሣሽ ትራንስፖርት ድርጅት ባለቤት አቶ ወ/ሚካአል ሃለፎም፣ የታደለ ብርሃኑ አስመጪና ላኪ ድርጅት ባለቤት አቶ ታደለ ብርሃኑ፣ ስራው ያልተገለፀውና እስካሁን በቁጥጥር ስር ያልዋለው አቶ ብርሃኑ ዝናቡ ሹመይ እንዲሁም የ24 አመቱ የ1ኛ ተከሣሽ ወንድም አቶ ካህሣይ ጉላን ዓለሙ ደግሞ በአንድ መዝገብ ተከሰዋል፡፡
በአቶ ተመስጌን ጉላን ላይ በተናጠል የቀረበው 1ኛው ክስ፤ ተከሣሹ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በተለያየ ሃላፊነት ላይ ተመድቦ ከ1999 ዓ.ም እስከ 2004 ዓ.ም ለስድስት ዓመታት ሲሠራ፣ አስቀድሞ በነበረበት የመንግስት ስራ ወይም በሌላ መንገድ ሲያገኘው ከነበረው ህጋዊ ገቢ ጋር የማይመጣጠን፣ በወንድሙ በካህሣይ ጉላን ስም በዳሽን ባንክ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ፤ በራሱ ስም ደግሞ በወጋገን ባንክ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በማስቀመጥ እና በማንቀሳቀሱ በአጠቃላይ በራሱና በወንድሙ ስም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ አስቀምጦ በመገኘቱ ተከሷል፡፡
ተከሣሹ በጓደኛው ብርሃኑ ዝናቡ ስም ስድስት ቦቴ መኪናዎችን ከነተሳቢያቸው፣ በአቶ ወ/ሚካኤል እና ታደለ ብርሃኑ አማካኝነት ከባንክ 10.5 ሚሊዮን ብር በመበደር ከራሱ 10.5 ሚሊየን ብር በመጨመር በድምሩ በ21 ሚሊዮን ብር ከሰኢድ ያሲን ኃላ.የተ.የግል ማህበር ገዝቶ መኪኖቹን በ2005 ዓ.ም ለተለያዩ ግለሰቦች በመሸጥ፣ በወንድሙ ስም ከቢዩ ኃ/የተ/የግ/ማህ ሁለት ዶዘሮችን በብር 15 ማሊዮን ብር መግዛቱ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በወንድሙ ስም በቦሌ ክ/ከተማ 325 ሜ.ካ ቦታ ላይ የተሠራ መኖሪያ ቤት በማፍራቱ እና በ2.8 ሚሊየን ብር በመሸጡም ተከሷል፡፡
ቀሪዎቹ ተከሣሾች ደግሞ፣ አቶ ተመስገን ሙስና ፈፅሞ ያገኘው ገንዘብ እና ንብረት መሆኑን እያወቁ መኪኖቹ የሚገዙበትን ሁኔታ ሃሣብ በማፍለቅና በመርዳት፣ የባንክ ብድር እንዲገኝ በማመቻቸት እና በመበደር እንዲሁም በራሱ አስመጪና የትራንስፖርት ድርጅት ስር መኪኖቹ ተጠቃለው እንዲሠሩ በማድረግ አቶ ወ/ሚካኤል ሃለፎም ተጠያቂ ሲሆን አቶ ታደለ ደግሞ በሙስና ወንጀል የተገኘው ገንዘብና ንብረት እንዳይታወቅ ለማድረግ አቶ ብርሃኑ ዝናቡ እና ካህሣይ ጉባል የቀበሌ መታወቂያ እንዲያወጡ በማመቻቸት እና በቀበሌው መታወቂያ መነሻነት የተጠቀሡትን ወንጀሎች እንዲፈፅሙ በማድረጉ  በወንጀሉ በመሣተፉ መከሠሡ ተመልክቷል፡፡ በቁጥጥር ስር ያልዋለው አቶ ብርሃኑ ዝናቡ፤ መኪኖቹ በስሙ እንዲገዙ፣ የባንክ ብድርም በስሙ እንዲበደር በማድረጉ ክስ የቀረበበት ሲሆን ወጣት ካህሣይ ደግሞ ለወንድሙ ውክልና ሠጥቶ በስሙ ገንዘብ እንዲያስቀምጥና እንዲያንቀሣቅስ እንዲሁም መኖሪያ ቤት እንዲገዛ በማድረጉ ተከሷል፡፡
ቀደም ብሎ በነበሩት ሁለት ቀጠሮዎች አቶ ተመስገን፣ አቶ ወ/ሚካኤል እና አቶ ታደሰ፤ ክሡ ተነቦላቸው መቃወሚያቸውን አቅርበው፣ አቃቤ ህግም ለመቃወሚያው መልስ የሠጠ ሲሆን ካህሣይ ጉላል ለመጀመሪያ ጊዜ ከትናንት በስቲያ ቀርቦ ክሡ ከተነበበለት በኋላ፣ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ከሌሎች ተከሳሾች ጋር አብሮ እያየው ነው፡፡
አቃቤ ህግ በተከሣሾቹ ላይ 14 የሠውና 14 የሠነድ ማስረጃዎችን ከክሡ ጋር አያይዞ አቅርቧል፡፡
ከትናንት በስቲያ የዋለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛው ችሎት፤ በመዝገቡ ላይ የተለያዩ ትዕዛዞችን ያስተላለፈ ሲሆን በእለቱ የቀረበው 5ኛ ተከሣሽ፤ የዋስትና መብቱ ተከልክሎ በቀጣይ ቀጠሮ ከጠበቃ ጋር እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት፣ መዝገቡን ለጥር 6 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡ -

Published in ዜና

መቀመጫውን በኒዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ቡድኑ /CPJ/  ባለፈው ረቡዕ  ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ ጋዜጠኞችን በማሰር ከአለም አስር አገሮች መካከል ኢትዮጵያን በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጠ ሲሆን ኤርትራ ቀዳሚ ሆና፣ ግብፅ በሶስተኝነት ተቀምጣለች፡፡
ሲፔጂ 34 አፍሪካዊ ጋዜጠኞች በሰሜንና ምስራቅ አፍሪካ በእስር ላይ እንደሚገኙ የገለፀው ሲፒጄ፤ በኢትዮጵያ ሰባት ጋዜጠኞች በጻፉት ጽሑፍ ሣይሆን “አሸባሪ” ተብለው በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
አለም አቀፍ የመብት ቡድን (Global rights group) የተባለው ተቋም በበኩሉ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞቹን ያሰራቸው ሚዲያውን ዝም ለማሰኘት ስለሚፈልግ ነው ብሏል። በኤርትራ 22 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙና አንዳቸውም ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ የገለፀው ሲፒጄ፤ እስረኞቹን በተመለከተ ከኤርትራ መንግስት ምንም አይነት መረጃ ለማግኘት እንደተቸገረ ጠቁሟል፡፡ ጋዜጠኞችን በማሰር የ3ኛ ደረጃን በያዘችው ግብፅም ጋዜጠኞች መታሰር የጀመሩት ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ ወደ ስልጣን ከመጡበት ቀን ጀምሮ ነው ብሏል ሲፒጄ፡፡ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች ተወካይ ቶም ሮዲስ በናይሮቢ ለCPJ እንደተናገረው፤ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የተለያዩ ችግሮች እንዳሉና መንግስታት ስለ ችግሩ መወያየት እንደማይፈልጉ ገልጿል፡፡ ሲፒጄ ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚዎቹ 10 አገራት በሚል ከዘረዘራቸው መካከል ቬትናም፣ ሶሪያ፣ ፓኪስታንና ቤልጂየም ይገኙበታል፡፡

Published in ዜና

ምእመናን ለሚከፍሉትና ለሚሰጡት ገንዘብ ደረሰኝ የመጠየቅ ልማድ ሊኖራቸው ይገባል
ድብቅ ሙዳየ ምጽዋት ማስቀመጥ፣ በዣንጥላና በምንጣፍ ገንዘብ መለመን ይከለከላል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት የካሽ ሬጅስተር ማሽንን ለገቢ መሰብሰቢያነት ለመጠቀም  ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ዘመኑን ያልዋጀውንና ጥራት የጎደለውን፣ ለሙስናና ብክነት የተጋለጠውን የቤተ ክርስቲያኒቱን የፋይናንስ አሠራርና ቁጥጥር ችግር፤ ግልጽነት፣ ወጥነት፣ ተቀባይነትና ተጠያቂነት ባለው የፋይናንስ አያያዝ ሥርዐት ለመቅረፍና ለማድረቅ ያስችላል፤ በሚል በቀረበው የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ አያያዝ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ረቂቅ ላይ እንደተጠቀሰው÷ በማንኛውም መንገድ የተሰበሰበ ገንዘብ፣ ሕጋዊ የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ወዲያውኑ ሊቆረጥለት የሚገባ ሲኾን ይህም በዋናነት በካሽ ሬጅስትር ማሽን እንደሚከናወን ተመልክቷል፡፡
የሀ/ስብከቱ አብያተ ክርስቲያናት የካሽ ሬጅስተር ማሽን ተጠቃሚ መኾናቸው፣ በገቢ ሒሳብ አሠራርና ቁጥጥር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመከላከል ያስችላል ተብሏል፡፡ በጥናቱ ላይ በመነሻነት ከተዘረዘሩት ችግሮች መካከል የዕለት ገቢዎችና ደረሰኝ አጠቃቀም ተጠቅሷል።  የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብ ገቢ ሰነዶች በሕገ ወጥ መንገድ አሳትሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ለግል ገንዘብ ይሰበሰባል፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተከለከለ ደረሰኝ ጥቅም ላይ የሚውልበት አጋጣሚ ታይቷል፤ ከደረሰኙ /ለከፋዩ ከሚሰጠው/ የተለየ መጠን በቀሪው ላይ መጻፍና የግል ጥቅምን ማካበት ይዘወተራል፤ ዘወትርና በክብረ በዓላት በርካታ ገንዘብ ገቢ ቢኾንም በዕለቱ ወደ ባንክ ያለማስገባት ኹኔታ አለ፤ ምእመናን ለሚከፍሉትና ለሚሰጡት ገንዘብ ደረሰኝ የመቀበል ልማድ የሌላቸው መኾኑን እንደክፍተት በመጠቀም፣ ለቤተ ክርስቲያን የመጣው ገንዘብ ‹‹በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት ይበዛል››፣ በሥራ ላይ ያልዋሉ የገንዘብ ገቢና ወጪ ሰነዶች (ሞዴላሞዴሎች ሴሪ ንምራ ቁጥር) መሠረታዊ ችግር ተጠንቶ መፍትሔ አልተሰጠም፡፡
በንግሥ፣ በወርኃዊ በዓላትና በዕለተ ሰንበት በሙዳየ ምጽዋት ሳይኾን በተዘረጋ ጨርቅ ላይ የሚሰበሰብ ገንዘብ መኖሩን የሚጠቅሰው ጥናቱ፤ በዚህ መልክ የተሰበሰበው ገንዘብ ሀ/ስብከቱ በታኅሣሥ፣ 2003 ዓ.ም. ባስተላለፈው የገንዘብ ቆጠራ፣ የንብረት አመዘጋገብና አጠባበቅ የሥራ መመሪያ መሠረት/ የምእመናንና ካህናት ሰበካ ጉባኤ ተወካዮች በሙሉ በተገኙበት ቆጠራ የማይካሄድበትና በተወሰነ መልኩም ሙሉ ገንዘቡ ገቢ የማይደረግበት ኹኔታ በመኖሩ አሠራሩ ለብኩንነት፣ ሐሜትና አሉባልታ መጋለጡን አመልክቷል፡፡ በንግሥ በዓላት ወቅት ጥላ ዘቅዝቀው የሚለምኑ ሰዎች ኹሉም ስለማይታወቁ የተኣማኒነት ችግር አለ፡፡ በስእለትና በሙዳየ ምጽዋት በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ የውጭ ሀገር ገንዘቦች፣ በመመሪያው መሠረት በዕለቱ የባንክ ምንዛሬ ወደ ብር እየተቀየሩ በተገቢው መንገድ ገቢ አለመኾናቸው፣ በምትኩ ቅያሬው ወጥነት ያለውና ለብኩንነት የተጋለጠ እንደኾነም ተገልጿል፡፡
በቃለ ዐዋዲ ድንጋጌው የተመለከተውንና በዝርዝር የሥራ መመሪያ የተላለፈውን የገቢ አሰባሰብ በተሻለ አሠራር ያጠናክራል የተባለው በፖሊሲና መመሪያ ረቂቁ የሒሳብ ሰነዶች አያያዝ፣ ምዝገባና አወጋገድ መሠረት÷ ለሒሳብ ሥራ የሚያገለግሉ ደረሰኞችና ቫውቸሮች የዋና ተጠቃሚውን ተቋም ስም ይዘው፣ በሀገረ ስብከቱ ምስጢራዊ ኮድ ይታተማሉ፤ የማሳተም ሓላፊነቱም የሀገረ ስብከቱ የፋይናንስና በጀት ዋና ክፍል ሲኾን ይህም በዋና ሥራ አስኪያጁ ፈቃጅነት የሚከናወን ይኾናል፡፡
በማንኛውም መንገድ የተሰበሰበ ገቢ ሕጋዊ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ወዲያውኑ ሊቆረጥለት ይገባል፤ ይህም በዋናነት በካሽ ሬጅስተር ማሽን ተፈጻሚ ይኾናል፤ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ከገንዘብ ሰብሳቢ ውጭ መያዝና መጠቀም አይቻልም። ማንኛውም የገንዘብ ስጦታ በገንዘብ ያዡ በኩል መሰጠት ይኖርበታል፤ ስጦታው እንደተበረከተም ወዲያውኑ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ሊቆረጥለት ይገባል፡፡ በዐይነት የሚሰጥ ስጦታ በግዥ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት በተተመነለት ዋጋ ይመዘገባል፡፡ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ውጭ በሙዳየ ምጽዋት ሣጥን ገንዘብ መሰብሰብ አይቻልም፤ ቋሚ ሙዳየ ምጽዋት በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን የሚቀመጥበት ቦታ ተጠንቶ፣ በሰበካ ጉባኤው መጽድቅ አለበት፤ ለቆጠራ ካልኾነ በቀር ከተቀመጠበት ማንቀሳቀስ አይቻልም፤ በትከሻና ተይዘው የሚዞሩ ሙዳየ ምጽዋት ሣጥኖች ሙሉ መረጃ ተመዝግቦ ይያዛል፡፡ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ በሚካሄድበት ወቅት ሣጥኖቹ ከመከፈታቸው በፊት ሁሉም ቆጣሪዎች የቁልፍ ካዝናውና የቁልፍ ሣጥኖች፣ የሣጥኖቹን ብዛትና እሽጋቸው አለመከፈቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፤ የተቆጠረ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ወዲያውኑ ካልተቻለ ከሌላ ገንዘብ ጋራ ሳይቀላቀል በበነጋው ወደ ባንክ አካውንት መግባት አለበት፤ ዣንጥላን፣ ምንጣፍንና የመሳሰሉትን በመጠቀም ገንዘብ መሰብሰብ ፈጽሞ የተከለከለ ይኾናል፡፡ዘመናዊው የፋይናንስ አሠራር በሀገረ ስብከቱ ተቋማትና አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲኾንም በተጭበረበሩ ደረሰኞችና በማይታወቁ የገንዘብ አሰባሰቦች የግል ጥቅምን ማካበት በመከላከል ለክትትልና ቁጥጥር አመች ለማድረግ እንደሚያበቃ ተመልክቷል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ በልማትና በጎ አድራጎት ተቋማቱ እንዲሁም በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚዘጋጁ የፋይናንስ ሪፖርቶች ግልጽነት፣ ወቅታዊነትና ተኣማኒነት/ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ሀገረ ስብከቱ በሚሰበሰበው የኻያ በመቶ ፈሰስና ከአብያተ ክርስቲያናቱ በቅጽ ተሞልቶ በሚላከው ሒሳብ መካከል በየዓመቱ የሚያጋጥመውን ልዩነት ለማስወገድ እንደሚያስችል ተገልጧል፡፡
ይህም በሒደት ከፍተኛ የሀብት ክምችት የሚገኝበት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በፋይናንስ አሠራሩና መልካም አስተዳደሩ የሁሉም አህጉረ ስብከት ሞዴል በመኾን ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ ማእከላዊ የፋይናንስና በጀት አስተዳደር ይኖራት ዘንድ መሠረት ለመጣል፣ የካህናቷን ኑሮ በማሳደግና በማሻሻል ሐዋርያ ተልእኮዋን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም የምትፈጥርበት መሠረት ለመጣል እንደሚያስችላት ታምኖበታል፡፡

Published in ዜና

ኮንሰርቱ በጥር ወር በድሬዳዋ ይጀመራል
ታዋቂው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “የፍቅር ጉዞ” የተሰኘ  ለአንድ አመት የሚዘልቅ የሙዚቃ ኮንሰርት ለመስራት ከበደሌ ስፔሻል ጋር ሰሞኑን የተፈራረመ ሲሆን ኮንሰርቱ ጥር ሶስት ቀን በድሬዳዋ እንደሚጀመር ተገለፀ፡፡
ቴዲ አፍሮ፣ ማናጀሩ፣ እንዲሁም የሄኒከንና የበደሌ ቢራ ስራ አስኪያጆች ትላንት በሂልተን ሆቴል በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የኮንሰርቱ የአንድ አመት ቆይታ ከቴዲ አፍሮ ጋር ታሪካዊና የተሳካ ይሆናል ብለዋል፡፡ “በደሌ ስፔሻል ቀደም ሲል ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድኑን (ዋልያን) ስፖንሰር በማድረግ ታሪክ ሰርቷል” ያለው ቴዲ አፍሮ፤ “እኔም ከበደሌ ስፔሻል ጋር የማደርገው የአንድ አመት የሙዚቃ ድግስ ጉዞ ታሪካዊ እንደሚሆን አልጠራጠርም” ብሏል፡፡
“የፍቅር ጉዞ” የሙዚቃ ድግስ ዋና አላማው፤ ኢትዮጵያዊያንን በፍቅር አንድ ማድረግ እንደሆነ የገለፀው ቴዲ አፍሮ፤ “ምንም እንኳን የተለያየ ቋንቋና ባህል ቢኖረንም አንድ አገር ውስጥ እንደመኖራችን የአለም ቋንቋ በሆነው ሙዚቃ ህብር ፈጥረን አንድ እንሆናለን” ብሏል፡፡ አርቲስቱ ከአቦጊዳ ባንድ ጋር የሚያቀርበው ኮንሰርት፤ በድሬዳዋ፣ ጂማ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ይካሄዳል ተብሏል፡፡ “ጥቁር ሰው” የተሰኘ አልበሙ ሲወጣ ስፖንሰሩ ሜታ ቢራ እንደነበር ያስታወሰው የቴዲ አፍሮ ማናጀር አቶ ዘካሪያስ ጌታቸው፤ ከሜታ ጋር በሰላምና በፍቅር ስራቸውን ጨርሰው ወደ በደሌ ስፔሻል መምጣታቸውን ገልጿል፡፡ በደሌ ስፔሻል ለአንድ አመቱ የሙዚቃ ድግስ ጉዞ ምን ያህል በጀት እንደመደበ ከአዲስ አድማስ ለቀረበው ጥያቄ የበደሌ ስፔሻል ስራ አስኪያጆች፤ “ጉዳዩ ምስጢር ነው፤ ይፋ አናደርግም” በማለት ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ የሄኒከን ማናጀር ሚስተር ዮሀንዱዌርስ ኮንሰርቱን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፤ በደሌ ስፔሻል፤ ታዋቂና ተወዳጅ ከሆነው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣ ጋር የአንድ አመት የፍቅር ጉዞ ለማድረግ ኩባንያቸው መወሰኑ እንዳስደሰታቸው ገልፀው፣ የቴዲና የበደሌ የአንድ ዓመት ቆይታ አይረሴ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡ ኮንሰርቱ በድሬዳዋ ከተጀመረ በኋላ ጅማ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባና ሌሎች ክልሎችን ያዳርሳል ተብሏል፡፡

Published in ዜና

በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ፣ ለቴሌ ታወሮችና የኔትዎርክ ግንባታ፣ ከጅቡቲ ተገዝቶ የገባው ሲሚንቶ ከአንድ ዓመት በፊት መበላሸቱ ቢታወቅም በወር ከ30ሺ ብር በላይ ለኪራይ እየተከፈለ በግለሰቦች ቤት እንደተቀመጠ ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የጅግጅጋ ቴሌ ቢሮ፤ ለታወሮችና የኔትዎርክ ግንባታ ሁለት ሺ ኩንታል የፓኪስታን ሲሚንቶ ከጅቡቲ ገዝቶ በማስመጣት በግለሰቦች ቤት በየወሩ ከ30ሺ ብር በላይ ኪራይ እየከፈለ ማስቀመጡን የሚናገሩት ምንጮች፤ የዛሬ ዓመት ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲሚንቶው ከጥቅም ውጭ እንደሆነ ቢረጋገጥም፣ እስካሁን ድረስ ለኪራይ እየተከፈለ ነው ብለዋል፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የመጋዘን ክፍሉ ሃላፊ በመኪና አደጋ ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ መጋዘኑ ተዘግ በመክረሙ ሲሚንቶው ለብልሽት ተዳርጓል ያሉት ምንጮች፤ ለዚህ ተጠያቂው የምስራቅ ጅግጅጋ ሪጅን ቢሮ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ይሄም ሳይንስ ቢሮው እነዚህን የተበላሹ ሲሚንቶዎችና ሌሎች ብረታብረቶች ያለምንም አገልግሎት በግለሰቦች ቤት አስቀምጦ፣ በወር ከ30ሺ ብር በላይ ኪራይ በመክፈል መንግስትን ለኪሳራ እየዳረገ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜም የሪጅኑ ቢሮ፤ ለታወሮችና ኔትዎርክ ግንባታ ከአዲስ አበባ ሲሚንቶ እየገዛ በመጠቀም ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡


Published in ዜና

ሀቢባ ከማል ትባላለች፤ በዱባይ ሀገር ለአስር አመታት ስትኖር አንድም ቀን ወደ አገሯ አልተመለሰችም፡፡ በቅርቡ ግን ሙሉ በሙሉ ጠቅልላ አገሯ ላይ ለመኖርና ጋብቻ ለመመስረት  አስባ ዕቃዎቿን እየሸከፈች ወደ አገሯ መላክ ጀመረች፡፡ ሀቢባ ይጠቅመኛል ያለችውንና በዱባይ ስትገለገልባቸው የነበሩትን ዕቃዎቿን የላከችው በወንድሟ እና በፍቅረኛዋ ስም እንደነበር ገልፃ፤ በፍቅረኛዋ ስም የተላከው እቃ ቢደርስም በወንድሟ ስም የተላከው እቃ አዲስ አበባ እንደገባ ተደውሎ ከተነገራት በኋላ “ጠፍቷል” መባሉን ትናገራለች፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ችግሩን ጉምሩክ ለኃላፊዎች መንገሯን የምትግልፀው ሃቢባ፤ መፍትሄ ግን አላገኘሁም ትላለች፡፡ እቃዎቹ መዋቢያዎችና በቀላሉ የሚበላሹ መገልገያዎች እንደሆኑ ገልፃ፤ የጠፉትን ንብረቶች ለማሟላትም ከዚህ አገር እየገዛች መሆኑንና ለኪሳራ መዳረጓን ትናገራለች፡፡
ሌላዋ ቅሬታ አቅራቢ ትዕግስት ሀለፎም በበኩሏ፤ ለአባታቸው የደም መለኪያና መድሃኒቶችን እህቷ በጉምሩክ በኩል እንደላከችላት ገልፃ፤ እቃው ደርሷል ተብላ ከተጠራች በኋላ ግን ማግኘት አለመቻሏንና ለስምንት ወራት መመላለሷን ትናገራለች፡፡ ጉዳዩን ለጉምሩክ ሃላፊዎች መናገሯንም ጠቅሳ፤ በካሜራ ስለሚታይ ምንም ዕቃ እንደማይጠፋና ማንም ሰራተኛ እንደማይነካ እንደተገለፀላትና እስካሁን ግን እቃዋን እንዳላገኘች ተናግራለች፡፡
ከእቃዎች መጥፋት በተጨማሪ ያለ አግባብ ቀረጥ እንደሚጫንባቸውም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ፡፡ ለስምንት አመታት በባህሬን ስትገለገልባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን ይዛ የመጣችው ሙሉ በሙሉ አገሯ ላይ ለመኖር በማሰብ እንደሆነ የተናገረችው አሰለፈች አማረ፤ ላመጣኋቸው እቃዎች 41 ሺህ ብር ቀረጥ ክፈይ ስባል ደነገጥኩ ትላለች፡፡ ምክንያቱን ስጠይቅ የሚያስረዳኝ አላገኘሁም ያለችው አሰለፈች፤ “እቃውን የገዛሁበት ዋጋ ቢደመር የዚህን ያህል አያወጣም፤ ስለዚህ ውሰዱት” ብዬ ትቼላቸዋለሁ ብላለች፡፡ ባለፈው ሰኞ ችግሮቻቸው እንደሚፈቱ እና ካሜራ ስለተገጠመ ምንም ዓይነት ስርቆት እንደማይካሄድ በጉምሩክ ሃላፊዎች እንደተገለፀላቸው የተናገሩት ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ እስካሁን ግን እቃቸውን እንዳልተረከቡ ጠቁመዋል፡፡

Published in ዜና

የሸራተን አዲስ ሆቴል ሰራተኞች፤ የውጭ አገር ዜጋ በሆኑት የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ የሚደርስብን ችግር ከአቅም በላይ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፍ ልንወጣ ነው አሉ፡፡ ከዚህ በፊት  የመብት ጥሰት እንደደረሰብን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤ ብንገልፅም ምላሽ ባለማግኘታችን በድጋሚ ደብዳቤውን አስገብተናል ብለዋል - ሰራተኞቹ፡፡
በትምህርት ደረጃና በእውቀት ከሀበሾቹ የማይበልጡ የውጭ ዜጐች አሰሪዎቻችን ያንቋሽሹናል፤ ዛሬ ፆም ነው ይህን አንበላም ስንል “ድሮ ረሀብተኞች ስለነበራችሁ ረሀባችሁን ለማስታወስ የምታደርጉት ነው” ይሉናል፤ ጥቅማጥቅሞቻችን አይከበሩም፣ እድገት እንከላከላለን ያሉት ሠራተኞቹ፤ “ፈረንሳዊው ስራ አስኪያጅ ዲፓርትመንቶችን በመበታተን፣ ሰራተኞችን ወዳልፈለጉትና ወደማይመለከታቸው ቦታ ይመድባሉ፤ ይህን ስንቃወም እስከመደብደብ እንደርሳለን” ብለዋል፡፡
“የዜጐች ደህንነት ጥበቃ ከአገር ውስጥ ይጀምራል፤ በአገራችን ነጮች እያንቋሸሹን እና ሞራላችን እየተነካ ነው” የሚሉት ሰራተኞቹ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ችግራችንን በዝምታ ማለፋቸው አሳዝኖናል ብለዋል፡፡
“ችግራችን ሲብስ ፒቲሽን ተፈራርመን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስገባነው ደብዳቤ፤ ለሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ለሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍ ከደረሰ በኋላ፣ ስቃያችን በዝቷል ያሉት ሰራተኞቹ፤ አንድ ነገር ለማስፈቀድ፣ አቤቱታ ለማሰማትና ለእድገት ለመወዳደር ስንጠይቅ ስራ አስኪያጁ  ፒቲሽን የፈረሙትን ሰራተኞች ስም ያወጡና “በእኔ ላይ ፈርመሀል፤ እድሜ ልክህን እድገት አታገኝም፣ ይህ አይፈቀድም” እያሉ እንደሚያንገላቷቸው ተናግረዋል፡፡ ሸራተን አዲስ ሆቴል ከ800 በላይ ቋሚ ሰራተኞች እንዳሉት የገለፁት ሰራተኞቹ፤ ይህ ሁሉ ሰራተኛ ባለበት ስራ አስኪያጁን ጨምሮ አንዳንድ የውጭ አሰሪዎቻችን እያንጓጠጡንና ጫና እየፈጠሩብን ስለሆነና የሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሽ ስላልሰጠን በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት አስበናል ብለዋል፡፡
የሆቴሉ ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበሩ አቶ ዳንኤል አለሙ ታሪኩ በበኩላቸው፤ “ሰራተኞቹ ከማህበሩ ወጥተው በራሳቸው ተደራጅተዋል፤ ነገር ግን ማኔጅመንቱና ሰራተኛው ተቀራርበው እንዲሰሩና በውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ብዙ ርቀት ብንሄድም የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍ ፈቃደኛ አልሆኑም” ብለዋል፡፡
የሆቴሉን ስራ አስኪያጅ  ሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍን ለማነጋገር ብንሞክርም እረፍት ላይ በመሆናቸው ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ ሌላ ሃላፊ ለማነጋገር ፀሃፊዋን ጠይቀን፤ በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጡት ስራ አስኪያጁ ብቻ እንደሆኑ ገልፃልናለች፡፡    

Published in ዜና

“ለሁለቱም እኩል ጊዜ ነው የሰጠነው፤ መካሰሳችንን ከአንቺ ነው የሰማነው” ኢትዮፒካሊንክ
“በስም ማጥፋት ሊከሰኝ የሚችልበት የህግ አግባብ የለም” - ወ/ሮ ቤተልሄም አበበ


በተለያዩ ፊልሞች፣ የመድረክ ድራማዎችና በተለይም በ “ገመና” አንድ ድራማ ላይ የዶ/ር ምስክርን ገፀ ባህሪ ወክሎ በመጫወት ተወዳጅነትን ያተረፈው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፤ “የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተውብኛል” በሚል በኢትዮፒካሊንክ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆች እና ወ/ሮ ቤተልሄም አበበ በተባሉ ባለሀብት ላይ ክስ መመስረቱን ለአዲስ አድማስ ገለፀ፡፡
“የዛሬ ሳምንት ምሽት ላይ ወ/ሮ ቤተልሄም አበበ፤ እኔን በሚመለከት በኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲያካሂዱ ነበር” ያለው አርቲስት ዳንኤል፤ ለዚህ ዘመቻቸው የኢትዮፒካሊንክ አዘጋጆች 15 ቀን ያህል ጊዜ ሲሰጡዋቸው፣ ለእኔ ግን ወደስቱዲዮ ሊገቡ ጥቂት ሰዓታት ብቻ ሲቀራቸው ደውለው፣ ስሜ ለጠፋበት ጉዳይ ምላሽ እንዳልሰጥ አድርገውኛል፤ በዚህም ክስ መስርቼባቸዋለሁ ብሏል፡፡
ከኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም አዘጋጆች አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ግዛቸው እሸቱን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግረነው በሰጠው ምላሽ፤ ለቅሬታ አቅራቢዋም ሆነ ለአርቲስቱ እኩል እድል ሰጥተናቸዋል፣ መከሰሳችንን ግን ገና ከአንቺ መስማቴ ነው ብሏል፡፡
ግንቦት 17 ቀን 2003 ዓ.ም በማስታወቂያ ድርጅቴ እና በካም ግሎባል ፒክቸርስ አማካኝነት ከአርቲስት ሀረገወይን አሰፋ ጋር “ፋየር ፕሩቭ” የተሰኘ የውጭ ፊልም ወደ አማርኛ መልሼ ለመስራት  ጀምሬ ነበር” ያለው አርቲስቱ፤ ይህን ፊልም በመሪ ተዋናይነት ከሀረገወይን ጋር ለመስራት ስምንት የፊልሙ ክፍሎች መቀረፃቸውን አርቲስቱ ይናገራል፡፡ በወቅቱ “የሴም ወርቅ” የተሰኘ ፊልም እየሰራ እንደነበር የተናገረው አርቲስቱ፤ በመሀል “ፋየርፕሩቭን”  መቅረጽ ያስፈለገበት ምክንያት አርቲስት ሀረገወይን ነፍሰጡር ስለነበረች፣ ከመውለዷ በፊት ትክክለኛውን እርግዝና ለመቅረጽ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ከዚህ በኋላ ጐንደር ቀረፃ ላይ እንዳለ በተደጋጋሚ ወ/ሮ ቤተልሔም መደወላቸውን፣ ስልኩን ባለማወቁና ስራ ላይ ስለነበር እንዳላነሳው የገለፀው አርቲስት ዳንኤል፤ ከ20 ቀን በኋላ አዲስ አበባ እንደተመለሰ ይሄው ስልክ በድጋሚ መደወሉንና ማንሳቱን አስታውሶ፤ “አብረን ፊልም እንድንሰራ እፈልጋለሁ” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጿል፡፡
“ስክሪፕት ስጭኝና አይቼ እወስናለሁ የሚል ምላሽ ሰጠሁ” ያለው አርቲስቱ፤ ወ/ሮ ቤተልሄም ስለ ፊልሙ ስክሪፕብት አንዳንድ ነገሮችን ሲነግሩኝ፤ እኔ ስምንት ክፍል የቀረጽኩት “ፋየር ፕሩቭ” መሆኑን አወቅሁኝ ሲል ገልጿል፡፡
“ወይ እኔ ልስራ አለበለዚያ እናንተ ስሩት” ብያቸው ነበር ያለው አርቲስት ዳንኤል፤ “አብረን እንስራው” በሚል ስምምነት ላይ መድረሳቸውንና  “በኋላ ግን ወ/ሮ ቤተልሄም፤ በስራዬ ጣልቃ እየገቡና የስነ ምግባር ጉድለት እያሳዩ በመምጣታቸው ስራዬን ለማቆም ተገድጄያለሁ” ያለው አርቲስቱ፤ ይህን ስላደረግሁ በሚዲያ ስሜን የማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል፤ ጉዳዩንም ወደ ህግ ወስጄው ህግ ይዞታል ብሏል፡፡
“እስከዛሬ የወ/ሮ ቤተልሄም ቤተሰብና ማህበራዊ ግንኙነት እንዳይረበሽ በሚል ብዙ ምስጢሮችን ይዤ ቆይቻለሁ” ያለው አርቲስቱ፤ በህግ የያዘው ጉዳይ ሲፈፀም ምስጢሮቹን ይፋ እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡
ኢትዮፒካሊንክን የከሰሰበትን ምክንያት የተጠየቀው አርቲስቱ፤ “ኢትዮፒካሊንክ የእኔን ስም በየደቂቃው ሲጠሩ፣ የወ/ሮ ቤተልሄምን ስም ላለመጥራት ጥንቃቄ ሲያደርጉ አስተውያለሁ፤  ይህም ሚዲያውን እኩል እንደማያገለግሉበት ያሳያል” በማለት መልሷል፡፡
ጋዜጠኛ ግዛቸው በበኩሉ፤ “ቅሬታዎቹ አግባብ አይደሉም፤ ስቱዲዮ ገብቶ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ እኛም መረጃዎችን የምናጣራው በራሳችን መንገድ ነው ለሁለቱም እኩል ዕድል ሰጥተናል፤ በህግ ክፍላችን በኩልም ያሰራል አያሰራም የሚለውን ለማጣራት ሞክረናል” ሲል ገልጿል፡፡ “እንደውም በሰባት አመት የስራ ጊዜያችን ያላደረግነውን፣ እሱ ምላሽ መስጠት ስላለበት አድርገናል” ብሏል፤ ጋዜጠኛ ግዛቸው፡፡
የቅሬታ አቅራቢዋን ስም አልጠቀሱም የተባለውን በተመለከተ ሲመልስም፤ “የግለሰቧ ስም ይነሳ አይነሳ አላስታውስም፤ ያም ቢሆን የውስጥ አዋቂ ዋና አላማው የታዋቂ ሰዎች ጉዳይ ስለሆነ የእርሱን ስም ጠቅሰናል” ብሏል፤ ጋዜጠኛ፡፡
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ወ/ሮ ቤተልሔም አበበ በበኩላቸው፤ “እኛ ስሙን አላጠፋንም፤ በስም ማጥፋት ሊከሰን የሚችልበት የህግ አግባብ የለም” ካሉ በኋላ “ገንዘብ ወስዷል፤ ለዚህም ማስረጃ ስላለን ካራማራ ፖሊስ ከሰነዋል፤ ቀሪውን በጠበቃዬ በኩል አጣሩ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

Published in ዜና
Page 7 of 16