አፍሪካዊያን በሕይወት ጉዞ ውስጥ ያለፉበትን ሂደት በመመርመር ፍልስፍናዊ ትንታኔዎችን በመጻፍ የሚታወቀው የሞርጋን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ፀናይ ሠረቀ ብርሃን፤ የአውሮጳ ፈላስፋዎች ለቀሪው የዓለም ክፍል ያላቸውን እይታ ይተቻል። የአውሮጳ አዙሪት ማለት ፣ድንበር አልባ የሆነ በዘመናዊነት አስተሳሰብ ውስጥ ስር የሰደደ የተሳሳተ የራስ ግምት ነው። “አውሮፓዊነት ከማንኛውም የሌላ አካባቢ ሰው የተለየ ፍጡር ነው  ብለን ስናስብ የአውሮፓ አዙሪት ውስጥ ነን ። ገና ካፈጣጠራችን ጀምሮ ከቀሪው ዓለም የላቅን ነን የሚል አመለካከት ላይ የተመሰረተ ሰብእና ነው የአውሮፓ አዙሪት ማለት” ይለናል ፀናይ። የአፍሪካ ፍልስፍና በምንለው ዘርፍ ውስጥ አንድ ብለን ልንቆጥረው የምንችለው አበሻ ፈላስፋ ፀናይ ሠረቀ ብርሃን ነው።
ይህ የአውሮፓ አዙሪት እንደ ፀናይ ገለጻ ከሆነ፣ እንዲሁ በቀላሉ በየሰፈሩ የሚወራ ብቻ ሳይሆን ደንበኛ ፍልስፍናዊ መሰረት ተሰጥቶት ፈላስፎች ሲሰብኩት የኖሩት ጉዳይ ነው። የአውሮጳዊውን ዘር ከፍ ከፍ የሚያደርግና ሌላውን የሰው ዘር የሚያንቋሽሽ ፍልስፍናዊ ጽሑፎች በስፋት ተሰርተዋል። አውሮጳዊ ሐሳቦችን እና የሐሳብ ቅርጾችን ማደናነቅና የሌላውን ማህበረሰብ እሳቤዎች ትቢያ ማድረግ የቅድመ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አባዜ ነበረ። አፍሪካዊያን፣ህንዳዊያን፣እስያዊያን እና የአሜሪካ የጥንት ባለርስቶች /ቀይ ህንዶች/ እነዚህ ሁሉም የአውሮፓዊ ፍልስፍና መሳለቂያ ከመሆን አላመለጡም። መሳለቂያ የሚያደርጓቸውም ዛሬም ድረስ በፍልስፍና ሐሳቦቻቸው የምናደንቃቸውና የምንፈራቸው ታላላቅ ሰዎች ናቸው። ፀናይ እነዚህን ዋርካዎች ነው የሚገነዳድሳቸው (የጦቢያቱ  ልጅ ማንን ይፈራል!)
ፍልስፍና “ይህን ዓለም የሚመራው አዕምሮ ነው” በሚል እሳቤ ላይ ተመስርታ፤ ለራሷ የሰጠችው ዓለማቀፋዊ ተልዕኮ አላት። እናም ፈላስፎች ለሰው ልጅ የሚበጅ ታላቅ ነገር እንደ ሚሰሩ ያስባሉ፤ ነገር ግን “ችሎት አምባ” የምናቀርብበት ሰዓት  አሁን ነው ይለናል፤ ፀናይ ሠረቀ ብርሃን። ባንድ ጎን አለማቀፋዊ ተልዕኳችን ለሰው ልጅ እርባና ያለው ስራ ማቅረብ ነው እያሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አውሮጳዊነትን ብቻ ከፍ ከፍ ማድረጋቸው ፍርደ−ገምድልነት ነውና ካሁን በኋላ ይህንን እንዲሰሩ መፍቀድ የለብንም ባይ ነው። የአውሮፓ አዙሪት የተጠናወታቸውን ጽሑፎች ከተደበቁበት ስርቻ እየፈለስን እያወጣን፣ የአውሮጳዊን የተሳሳተ የኅላዌ ግንዛቤ በማጋለጥ የአፍሪካን ፍልስፍና እንጠብቅ/እንከላከል።
አማኑኤል ካንት፤ በታሪክ ነክ ፖለቲካዊ ጽሑፎቹ ውስጥ፤ሔግል “በመብት ፍልስፍና” እና “በታሪክ ፍልስፍና” ስራዎቹ እንዲሁም ካርል ማርክስ በኮሚኒስት ማኒፌስቶ ስራው የአውሮፓን “ዘመናዊነት” እውነተኛው የሰው ልጅ ዘመናዊነት አድርገው ሲያቀርቡት፤ የሌላውን ክፍለ ዓለም ዘመናዊነት ግን ግልብ፣መሰረት የለሽ ያደርጉታል። ለፈላስፎቹ ዘመናዊነት ማለት ግዛትን ማስፋት ወይም ኮሎኒያሊዝም ማለት ነው፤ይለናል ፀናይ። ዘመናዊነት በሚከሰትበት ወቅት ሁሉ ነባር እምነትን ሳይንድ መከሰት አይችልም፤ በሃቅ ውስጥ ያለን የሃቅ እጦት ያጋልጣል፤ የሌሎችን እውነታ መውረር/ማስገዛት ስራው ነው። የአውሮፓው ዘመናዊነት ዓለምን በአምሳሉና በአርያው ለመፍጠር የተቀረውን ዓለም ማህበራዊ ስሪት እንኩትኩቱን አውጥቶ አስገዝቶታል። የሌሎችን የህይወት እውነታዎች አርሳ፣ገልብጣ፣አበስብሳ የእራሷን የአውሮፓን እውነታዎች በመትከል አውሮፓዊነት በዓለም ለመሰራጨት ችላለች።
ኢምፔሪያሊዝም ኅልዮት ሲሆን ኮሎኒያሊዝም ደግሞ የተግባር መገለጫው ነው፤ በዚህም መሰረት ጥቅም  ላይ ያልዋለ ያልተገዛን ድንበር ሁሉ ወደ አውሮፓዊ ከተሜ ማህበረሰብነት በመለወጥ ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ። አንዳንዱን ቀደምት ነዋሪዎች አስወግዶ ሌሎችን ግን በተከለለ ቦታ እንዲኖሩ ማድረግ አሊያም ከገጠር እንዳይወጡ ማገድ አሊያም ከተማ እንዳይመጡ መከልከል። ይህንን እና መሰል የአገዛዝ እርምጃዎችን በመውሰድ ለቆጠራም፣ለግብር ስብሰባም፣ለብዝበዛም እንዲመቹ ማድረግ። በዚህ መልኩ አውሮፓ እራሷን በዓለም ላይ እያስፋፋች አፍሪካን፣እስያን፣አሜሪካን መቆጣጠር ችላለች። በዚህም ስራዋ ምንም ጥፋት እንዳልተከናወነ ማሳመኛ ፍልስፍናዎችን መደርደር ተያያዘችው። የሳይንስ፣የግብረገብ እና የጠቅላላ ፍልስፍና ሙግቶች ሁሉ እየተዘረዘሩ የአውሮፓን የጉልበት እንቅስቃሴ እንደ መደበኛ ጉዳይ እንድንቆጥረው ወተወቱ።
አውሮፓ የተቀረውን ዓለም  የማሰልጠን ኃላፊነትን ለራሷ አሸክማ፣የሌሎችን ነጻነት እና ሉዓላዊነት እንደልቧ ለመገርሰስ ያመቻት ዘንድ ስልጣኔን አስፋፋለሁ ትላለች። “ስልጣኔን የማስፋፋት ተልዕኳችን ብቻ የቅኝ ግዛትን ለማስፋፋት ማሳመኛ ነጥብ ይሆነናል” ይሉ ነበር እንደነ ፕላሲት ቴምፕል ያሉት ሚሲዮኖች። ሬድዮናችን፣ጽሑፋችን፣ትምህርታችን ሁሉም ደጋግመው አፍሪካን ማሰልጠን እንዳለብን ይሰብካሉ። ከህዝቡም መካከል ስልጣኔ ማለት የቁሳቁስ ቁጥር መብዛት፣የሙያ መስክ ክህሎት፣የቤት ግንባታ፣ንጽህና እና ትምህርት ሥርዓት የሚመስላቸው በብዛት አሉ፤ይሉናል አውሮፓዊያን። ይህ ሁሉ መልካም እሴት ነው፤ ነገር ግን ስልጣኔ ማለት ይህ ብቻ ነው? የሰው ልጅ መንሰራፋት እና መስፋፋት ማለት አይደለም እንዴ? ፀናይ መልሶ ይጠይቃል።
ኪፕሊንግ በጣፈጠ ቋንቋ እንዳስቀመጠው፤ “የአውሮፓ ቅኝ ግዛት ተልዕኮ ግማሽ አውሬ ግማሽ ሰው የሆነውን ገጠሬ ማህበረሰብ ‘ሰው ሰው እንዲሸት’ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነበረ።” አውሮፓ እራሷን የሁሉም ነገር መለኪያ አድርጋ በመቁጠር፣ የሌሎች እውነታ አልታያት ብሎ “በእውነታ ውስጥ እውነታ ጎድሏል” ትል ነበር - ‘lack of reality in reality’። ጽድቅን ማስፋፋት፣ስልጣኔን ማዳረስ፣መላውን ዓለም በአውሮፓ መስፈርት አውሮፓዊ ማስመሰል የቅድመ ሃያ አንደኛው የአውሮፓ ፍልስፍና ነበረ። አውሮፓ ከነግሳንግሷ እራሷን በዓለም ላይ ቅኝ ግዛት እንድትጭን ፍልስፍና ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። የካንት “ከድንቁርና መንጻት” እና “በእውቀትና በእኩልነት መፈወስ” ትርክት፤ እንዲሁም የሔግል “አለማቀፋዊ እሳቤዎችን መከወን”፤ እናም የማርክስ “በማህበረሰባዊ ስራ ከጭቆናና ከባይተዋርነት ነጻ መውጣት” ትምህርቶች ለዚያ ዘመኗ አውሮፓ፣ እንደ ጉሽ ጠጅ በኃይል ላይ ኃይል እየሰጧት ዓለምን ወረረች።
አለማቀፋዊ ነጻነት፣ የሰው ልጅ ምልዑነት፣የሰው ልጅ መንሰራፋት የሚሉት ሐሳቦች አውሮፓን የታሪክ ባለቤት ለማድረግ የሚቀርቡ በፍልስፍና ውስጥ ያሉ ቅድመ ጽሑፎች ናቸው /the text that comes before the text of humanity/(ወይም ደግሞ በለመድነው አማርኛ “ስውር ደባዎች” ናቸው ማለት እንችላለን)። እንዲህ ያሉ ድብቅ አጀንዳዎችን በማምረት ደግሞ አማኑኤል ካንትን የሚያክለው የለም። ይህንን ሐሳብ ፍሬድሪክ ኒቼ እና ሚሼል ፉኮ ይጋሩታል፤ “የሰው ልጅ” ሲል ካንት ምን ለማለት ፈልጎ ነው ይለናል ፉኮ (እንደ ዛሬዎቹ የቋንቋ (ደንቆሮ) መምህር ነን ባዮች ሳይሆን፤የቋንቋ ፈላስፋው ፉኮ ከፈረስ ጭራ የቀጠኑ ሐሳቦችን የሚረዳ ፈላስፋ ነበረ)። የሰው ልጅ በዘመነ አብርሆት ውስጥ ነው እያለ ካንት የሚያውጀው የትኛውን የሰው ልጅ ነው? የካንት የሰው ልጅ የሚለው ብያኔ አውሮፓን ብቻ የሚወክል ስለሆነ ችግር ያለበት ብያኔ ነው ይለናል ኢትዮጵያዊው  ፀናይ። ይህ አልበቃው ብሎ እንደውም እቅጩን ሲነግረን “የአፍሪካ ጥቁሮች በተፈጥሯቸው ከእንጭጭ ስሜት ውጭ ምንም የላቸውም” ይለናል ካንት። ተራ ግርድፍ ስራዎችን/ሐሳቦችን መከወን ይችሉ እንደሆነ እንጅ የረቀቀና የጠራ ስራ/ሐሳብ መከወን የሚችሉ አይደሉም ጥቁሮች፣ እንደማለት ነው - የካንት ሐሳብ።
አቶ ሔግልም በተራው ከአፍሪካዊያን/ኒግሮ መካከል አንድ ተሰጥዖ ያለው ቢገኝ አሊያም ስነ ጥበብ፣ሳይንስ፣ሌላም ዋጋ ያለው ችሎታ ያለው ቢገኝ “ጸጉር ከምላሴ ይነቀል” ይለናል። “ብዙ ነጮች ከታችኛው ማህበረሰብ ተነስተው እራሳቸውን ሲለውጡ እናስተውላለን፣ ነገር ግን ነጻ ከወጡት ጥቁሮች ውስጥ እንኳን አንድም ኒግሮ ሲሻሻል አይተን አናውቅም፤ ነጩ ግን በተለየ ክህሎቱ በዓለም ክብር ሲያገኝ እያየነው ነውና አዕምሮው ብቻ ሳይሆን የቆዳ ቀለሙም የተከበረ ነው” ይላል ሔግል። ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው ይባላል፤ ይኸውላችሁ ቀስ እያሉ ልክ ልካችንን እየነገሩን ነው የተከበሩት ፈላስፎቻችን። የሔግል ድምዳሜ ደግሞ የባሰበት ነው (ጽንፍ የያዘ )፤ የሰው ደረጃው እንደ የቆዳው ቀለም ጥቁረትና ንጣት መጠን  ይለያያል ሊለን ትንሽ ነው የቀረው (ኧረ እንደውም ከዚህ በላይ ሳይሆን አቀርም አባባሉ)። ነጭ ሰው ቢወድቅም ተፍጨርጭሮ ይነሳል፤ እራሱንም ከትላልቆች እኩል እስኪያደርስ ይጥራል። ጥቁር የሆነ እንደሆነ ግን በባርነት ቢሸጥም ያው ባሪያ ነው፤ ከባርነት ነጻ ብንለቀውም ከባርነት ዘመኑ የተሻለ ምንም ነገር አይሰራም። የነጭንና የጥቁርን ሰው የተፈጥሮ ልዩነት በዚህ ማየት እንችላለን እንደ ማለት ነው፣ ጋሽ ሔግል የሚለን።
አብርሆት ምንድን ነው? (‘What is Enlightenment?’) በሚለው የካንት ስራ ውስጥ እራሳችንን ከገባንበት ድቀት እና ባዶነት ነጻ ማውጣት ማለት ነው ይለናል። ነጻ ለመውጣት ደግሞ እራስን መገምገም/መተቸት፣እራስን መጠየቅና መልሱን መፈለግ ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው። አመክንዮ እና ተጠየቅ ላይ ተመስርተን ያለንበትን ዘመን መገምገም ነጻ ለመውጣት መተኪያ የሌላቸው መፍትሄዎች ናቸው ይለናል - ካንት። ችግሩ የሚፈጠረው እነዚህን  ክህሎቶች እና ጸጋዎች አውሮፓዊ ማድረጉ ነው። ለካንት ጥቁር ማለት እንጭጭ ስሜቶችን ከማስተናገድ ባለፈ፤ የአመክንዮና የተጠየቅ ስልቶችን የመጠቀም ተፈጥሯዊ ብቃት የለውም፤ስለሆነም ወደ ብርሃን ዘመን መምጣት የሚችለው ነጭ እንጅ ጥቁርማ ስንኩል ነው ይለናል።
ፀናይ ሠረቀ ብርሃን፤ እነዚህን የተከበሩ ፈላስፎች ሐሳቦቻቸውን ከፍ ዝቅ እያደረገ  እያብጠረጠረ የአፍሪካ ፍልስፍና ብለን ስናስብ ያለፉ ደባዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት መሆን እንዳለበት የሚያሳስበን፤ እንዳንዶቹ  አበሾች ለሆዱ ማደር ተስኖት እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል። አውሮጳ እና ፈላስፎቿ በመስመር መካከል በቀጫጭኑ፣ እንዲሁም በእብሪት ባደባባይ የጻፉብን የሞት መልእክቶች ይዘውን ገደል እንዳይገቡ፤ በማንገዋለያ  እያንገዋለልን ምርቱን ከግርዱ መለየት የኛ የቤት ሥራችን መሆን አለበት። አንድ ዘመን ላይ አውሮፓ በራሷ ፍቅር አዙሪት ውስጥ ገብታ ያስመለሳት ቅርሻት፣ ለዛሬ ህይወታችን ጥላሸት እንዳይሆነን መጠንቀቁ የሚበጅ ምክር ይመስላል። ለፀናይ ግን ይህ ብቻ አይበቃውም፣ ለቀጣዩ ቸር ያሰንብተን።

Published in ጥበብ

ከጥንተ ሲናዊው የፊንቃውያኑ ፊደል ተገኝቷል፤ ከፊንቃውያኑ ካድመስ የተባለው ሰዋቸው ግሪኮች ፊደላቸውን ሰጥቷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል (ኤትሩስካኖች) የተባሉ በሮም ሰሜናዊ ክፍል የሰፈሩ ነገዶች ነበሩ። እነሱም “ኤትሩስካን” የተባለ ፊደል ነበራቸው። ከግሪክ እና ወይም ከኤትሩስካን የላቲን ፊደል ተወልዷል፣ ከላቲን ደግሞ የዛሬዎቹ አውሮጳውያን ቋንቋዎች ለሁሉ መጻፊያ የሆነው ሮማዊ የጽሕፈት ሥርዓት ተገኘ፡፡

ከግእዝ የመጡትን የአማርኛ ፊደላት ለመነካካት ሰበብ የሚደረገውን የሞክሼ ፊደላትን ነገር  እንድናነሳ ግድ እየኾነ “እንደገና ፊደል እንደገና” በማለት ከዚህ በፊት አንድ ጽሑፍ አቅርቤ ነበር። “ለመሆኑ እነዚህን ሞክሼ ፊደላት የተመለከቱ የፊደል መነካካቱን ጥያቄ (እነሱ ማሻሻል ይሉታል) በምን ምን ምክንያት ነው የሚጠይቁት” በማለት አንድ በአንድ እያነሳሁ የተመለከትኹበት ነበር፡፡
እነዚያ ሞክሼ ፊደላት ቢነካኩ (ቢጐድሉ) የሚያጐድሉብንን ለማስከተል ረዘም ያለ ጽሑፍ፣ በተለይም ሥነ ልሳን ፊደላትን የድምጽ ምልክቶች አድርጐ ብቻ ለምን እንደሚመለከታቸው በመጠየቅ፣ ጽሕፈት ከትእምርተ ድምፅነት ሌላ በርከት ያሉ ውክልናዎች ወይም ይዘቶችና አገልግሎቶች እንዳሉት በመጠቋቆም፣ ፊደላቱን ማጉደል እነዚያን ማሳጣት መሆኑን የሚገልጸውን አንድ ክፍል እያዘጋጀሁ ሳለ፣ የበፊቱን ካነበቡ ሰዎች የተለያዩ መልእክቶች በኢሜል አድራሻዬ ይመጡ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ተጨማሪ የሚፈልጉ፣ አንዳንዱ “ፖስት” እና “ትዊት” አድርገው የሚሉ ነበሩ፡፡
ሁለት አንባቢዎች ግን በፊደላቱ ላይ የተሠሩ ሥራዎችን አባሪ ያደረጉባቸውን መልእክቶች ነበር የላኩልኝ፡፡ አንደኛው የዶክተር አየለ በከሬን “ኢትዮፒክ” የተባለውን መጽሐፍ እንዳለ ነበር የላከልኝ፡፡ “መጽሐፉን ባጋጣሚ አግኝቸው ላንተም ይጠቅማል በማለት…” ብሎ ላከልኝ (ምስጋናዬን ለአቤል እዚህም ላይ ደግሜ አቀርባለሁ)፡፡ የዶክተር አየለን መጽሐፍ የሚዳሰስ ጽሑፍ፣ ከእርሳቸው ጋር የተደረገ ቃለምልልስ፣ እንዲኹም ያን መጽሐፍ ለመጻፍ ምክንያት የኾናቸውን ከግእዝ የተወሰደውን የአርመኖችን ፊደል የተመለከቱ ሥራዎችን በመጠኑ በመተርጐም በዚችው አዲስ አድማስ ያቀረብኩት ከመኾኑም በላይ፣ በ2005 ዓ.ም መጽሐፉን በአማርኛ እንዲተረጐም ሰጥተውኝ ሰርቼ አስረክቤአቸዋለኹ፡፡
አብዛኛው መነሻ ሐሳብ ከዚሁ ከአየለ በከሬ     “ኢትዮፒክ” የተገኘ የሚመስለውን ሌላውን ግሩም የጥናት ወረቀት አባሪ ተደርጐ የተላከበት ሁለተኛው መልእክት ደግሞ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
“ፍቅሩ ተምትም፣ ሃይ ሰሎሞን፣ የኢትዮጵያው ሥርዓተ ጽሕፈት ወዳጄ አሁን በቅርቡ የግእዝን ጽሕፈት የሚመለከት ድንቅ ወረቀት (የጥናት) አገኘኹ፡፡ ደሴ (በ10፡00 P.M) ስለ ጽሕፈቱ የትመጣ እንዲኹም ከሮማዊው ሥርዓተ ጽሕፈት አኳያ ያለውን ቁብ የሚመለከት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያላገኘኸው ከሆነ እንደሚጥምህ በማሰብ ላክሁልህ።
“ጥናታዊው ወረቀት የግእዝ ጽሕፈት በትእምርተ ሥዕልነቱ፣ በትእምርተ ከፊለቃልነቱ (syllographic)፣ በትእምርተ ፈለክነቱ፣ በስነ ኁልቁነቱ እና በትእምርተ ሐሳብነቱ የሚኖሩትን ረቂቅ እሴቶችና ባሕርያቱን ይገልጻል፡፡
ኾነ ብሎ እነዚህን ፊደላት መለወጡ እነዚህን እና የአባቶቻችንን ጥንታዊ እውቀት፣ ጥበብና ፍልስፍና ወደማሳጣቱ ያደርሰናል፡፡ ስለዚህ ነገር የበለጠ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ ረገድ አንተ የምትለውንም ባነብብ ደስ ይለኛል፡፡ የጽሕፈት ሥርዓታት በጊዜ ሒደት የመለወጣቸውን ነገርስ ትቀበለዋለህ? ከሆነስ እንደነ ዶክተር በዕድሉ ዋቅጅራ ያሉት የሚያቀርቡት ሐሳብ ምን የተለየ ኢምፓክት ያመጣል? አመሰግናለኹ፡፡
ከዚህ መልእክቱ ጋር የላከልኝ ወረቀት “ዩዜጅ ኦፍ ዘ ግእዝ ራይቲንግ ሲስተም ኦፍ ኢትዮፕያ” የሚል፣ ጋብሪኤላ ኤፍ ሴልታ በተባሉ ምሁር የተሠራ ጥናታዊ ወረቀት ነው፡፡
ንጽጽራዊ የግእዝ ሥርዓተ ጽሕፈትን የአውሮፓውያን መጻፊያዎችን ካስገኘው ሮማዊ አልፋ ቤት ጋር በንጽጽር የሚያቀርብ ጥናታዊ ሥራ ነው፡፡ ምልከታው ጥሩ ሆኖ ስለታየኝ፣ ጀምሬው ከነበረው ጋር አዋድጄ ለሁላችንም እንዲሆን ማድረጉን መረጥሁና የጀመርኩትን እንዳለ በመተው ከፍቅሩ ተምትም ወረቀት በጥቂቱ በቀጥታ እያቀረብኹ እና አስፈላጊ በሆነበትም በመግባት አዘጋጀሁት፡፡  እንዲህ ይነበባል፡-
“የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲሁም የሮማዊውን አልፋ ቤቶች የዕድገት ሒደት እናም የአሁኑን አጠቃቀም ለማወቅ የግእዝ ሥርዓተ ጽሕፈትን ማጥናት (ማወቅ) ያስፈልጋል፡፡ እንዲህም ሲባል የዛሬ ዘመኖቹን የምዕራባውያን አልፋ ቤቶች ከጥንታዊዎቹ ሥዕላዊ ፊደላቶች ጋር የሚያገናኘው ድልድይ የግእዝ ሥርዓተ ጽሕፈት ብቻ ነው ማለትም አይደለም”
ሁለቱም የጽሕፈት ሥርዓቶች፤ ሥራቸውን የጥንቱ ግብፃዊ ሂየሮግሊፍ በማድረግ፣ ከዚህ እንደተገኙ ለመቁጠር፣ ጥንተ ሲናዊ ጽሕፈት ያነሳል። እዚህ ላይ “ፕሮቶሺናዊ” የሚባለው ከግእዙ ጋር አንድ ሆኖ መገኘቱ በመታወቁ፣ ይህም ከግብፃዊው ሂየሮግሊፍ እንደተገኘ በመቁጠር፤ ሮማዊው ደግሞ ከጥንተሲናው በፊንቃውያን፣ በግሪክ፣ በላቲን በኩል የተገኘ በመሆኑ ይኸንኑ በመያዝ ነው እንዲህ የተገለፀው፡፡ በእርግጥም የሮማዊውን ጽሕፈት እስከ ጥንተሲናዊው ድረስ ወደ ላይ ሐረጉን መቁጠር ይቻላል፡፡ ወይም ከጥንተ ሲናዊ ጀምሮ በመውረድ እንደምን ሆኖ ከሲናው የመጀመሪያ ጽሕፈት ጋር እንዴት እንደሚገናኝ፣ በጽሑፉም እንደቀረበው፣ ማየት እንችላለን፡፡
ከጥንተ ሲናዊው የፊንቃውያኑ ፊደል ተገኝቷል፤ ከፊንቃውያኑ ካድመስ የተባለው ሰዋቸው ግሪኮች ፊደላቸውን ሰጥቷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል (ኤትሩስካኖች) የተባሉ በሮም ሰሜናዊ ክፍል የሰፈሩ ነገዶች ነበሩ፡፡ እነሱም “ኤትሩስካን” የተባለ ፊደል ነበራቸው፡፡ ከግሪክ እና ወይም ከኤትሩስካን የላቲን ፊደል ተወልዷል፣ ከላቲን ደግሞ የዛሬዎቹ አውሮጳውያን ቋንቋዎች ለሁሉ መጻፊያ የሆነው ሮማዊ የጽሕፈት ሥርዓት ተገኘ፡፡
በሌላ በኩል፤ በተለይ ከኤፍራጥስ-ጢግረስ ወንዞች በስተግራ ለሚገኙ አብዛኞቹ ጽሕፈታት አባት ተደርጐ የሚቆጠረው ጥንተ ሲናዊው ራሱ ከግእዝ ፊደላት ጋር ያለው መመሳሰል በግልጽ የሚታይና በዶክተር አየለ ቢከሬ የምርምር ሥራም የተረጋገጠ በመሆኑ፣ በዚህ ጥናት ደግሞ ግእዝ በቀጥታ “ከሂዩሮግሊፍ ወረቀት” ስለሚል የሁለቱም ሥር ሂየሮግሊፍ ድረስ የሚሄድ አድርጐ ያቀርባቸዋል፡፡ ጥያቄ የሚኖረው ጥንተ ሲናዊው ግእዝና የሂየሮግሊፍ ልጆች መኾናቸው ላይ ይሆናል፡፡
ለዚህ ድምዳሜ የሚያበቃ አንድ ነጥብ ቢኖር፣ ሂየሮግሊፍ የተባለው የጥንት ግብፃውያን መጻፊያ በ3000 ቅ.ል አካባቢ ላይ ይጻፍበት እንደነበር የአርኬዎሎጂ ማስረጃ መኖሩ፣ ለጥንተ ሲናው ደግሞ፣ ይኼው ጽሑፍም ሆነ በአመዛኙ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛው ዋቤ የሆነው የዶክተር አየለ በከሬም መጽሐፍ የጠቆሙት የአርኪዎሎጂ ግኝት የ1500 አመት ቅ.ል የተገመተ በመሆኑ፣ በታሪክ ዘመን መቀዳደማቸውን በዋነኝነት የያዘ፣ በተጨማሪም የሁለቱ ጽሑፎች መገኛ ቦታ አንድ እንደሆነ ለመግለጽ የተሞከረበት ዓይነቱ አንድ ሆኖ ቢገኝ እንኳ ብዙም አያወላዳም፡፡
በዘመን ቅደም ተከተል ከተሔደ፣ ይህ ጽሑፍ የሳተው አንድ ሌላ ጽሕፈትም በዚሁ አካባቢ ከሂየሮግሊፍ ያነሰ፣ ከጥንተ ሲናው የበለጠ ዕድሜ የተሰጠው መግባት ሊኖርበት ነው፡፡ ይህም “ሂየሬቲክ” የተባለው ጽሑፍ ነው፡፡ ለሂየሬቲኩ ከሂየሮግሊፍ አንድና ሁለት መቶ ዘመን አነስ ያለ ዕድሜ የተሰጠው የአርኬዎሎጂ ማስረጃ አለው። ስለዚህ ሂየሮግሊፉ ሂየራቲኩን ሂየራቲኩ ጥንተ ሲናዊውን አስገኘ ማለት ነበረበት፡፡
በመሠረቱ የዘመን መቀዳደሙ ጉዳይ የከርሠ ምድሩ ማስረጃ መገኘት ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ከጥንተ ሲናዊው እንደወረደ የሚገለጽ አንድ የመካከለኛው ምሥራቅ ጽሕፈት ከልደት በፊት 1800 አመት ተገምቶ ይገኛል፡፡ የጥንተ ሲናው እድሜ ከዚህ ያነሰ ሆኖ (1500 ቅ.ል) እያለም ነበር ያንኛው ከሲናው የወረደ እንደሆነ የተገለፀው፡፡
ጥንተ ሲናው የዶክተር አየለ በከሬ መጽሐፍ እስከሚታተምበት ድረስ (በ.1996) የነበረው የጥንተ ሲናው ግኝት የ1500 ቅ.ል. ያስቆጠረ ነበር። ዛሬ ሲና ተብላ በምትጠራው የስራ ቤት የከርሠ ምድር ማስረጃ ብቻ ነበር፡፡
መጽሐፉ ከታተመ በኋላ ሁለት አመት ቆይቶ፣ በመኻል ግብጽ፣ በአባይ ሸለቆ ውስጥ ሌላ ሁለተኛ የዚሁ ጽሕፈት የከርሠ ምድር ግኝት ተገኝቷል፡፡ የዚኸኛው ዕድሜ ደግሞ ከበፊቱ ላይ 200 አመት ያህል ጨምሮበታል፡፡
(ይህ ጽሑፍ ግን በ2001 (እ.ኤ.አ) ቢሠራ ከሁለት አመት በፊት የተገኘውን አዲስ ግኝት ሳይጨምር በቀጥታ ከዶክተር አየለ በከሬ እንደተገኘው የ1500 አመት ዕድሜን ብቻ ይዞ ነው የሚገኘው፡፡ ይህም ስለ ጽሑፉ አስቀድመን እንደጠቆምነው የዶክተሩን መጽሐፍ ብቻ በዋነኝነት መጠቀሙን ያመለክታል።)
ዋናው ጉዳያችን ግን የዘመኑ ጉዳይ እንዲህ ሲገኝ የሚቀየር በመሆኑ፣ አንደኛው ከአንደኛው የቀደመ ዘመንን ያስቆጠረ የከርሠ ምድር ማስረጃ ስላለው፣ ያንኛው ይኸኛውን አስገኘ ማለቱ እምብዛም አያስተማምንም፡፡
ግእዝም ሆነ ጥንተ ሲናዊው የሂየሮግሊፍ ውላጆች ናቸው ማለቱ በዚህ ረገድ ታይቶ ከሆነ አያስተማምንም፡፡ ምሑራኑም የሂየሮግሊፍ ለጥንተ ሲናው ወላጅ አባትነት ላይ ቁርጥ ያለ ድምዳሜ ላይ አልደረሱም፡፡ በተለይ በግእዝ የትመጣ ላይ ዶክተር አየለ፤ ግብፃዊው ጽሕፈት ከተገኘበት በተለየ አካባቢና ባህል የተገኘ መሆኑን ፊደላቱ ራሳቸው እንደሚመሰክሩት እነዚህኑ ሁለት ጽሕፈቶች በንጽጽር ባቀረቡበት ገጽ ይጠቁማሉ፡፡
ስለዚህ በዚህ ጥናታዊ ወረቀት የግእዙም ሆነ የሮማዊ ሥር ሂየሮግሊፍ እንደሆነ የተገለፀበትንና ከዚህ በኋላም ይህንኑ በመያዝ የሚገለፀውን በጥያቄ ምልክት ማለፉ ይሻላል፡፡
የጥናት ወረቀቱ ከዚህ ዓይነቱ ጥቆማው በማስከተል የሮማዊውን ጽሕፈት በየዐረፍተ ዘመኑ ያሳያቸውን ለውጦችና ዕድገቶች ያቀርባል፡፡
ሮማዊው ጽሕፈት ከልደት በፊት 600 አመት ላይ 21 ፊደሉን (5ቱን የግሪክ ዋየሎች ጭምር) ይዞ ተጀመረ፡፡ ያን ጊዜ አጻጻፉ ከግራ ወደቀኝ ሔዶ ሲያበቃ፣ ከቀኝ ወደ ግራ እንደሚመለስ፣ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ እንደገና ከግራ ወደቀኝ እያለ የሚጻፍበት ነበር፡፡ (ባውስትሮ ፌዶን” የሚሉት ዓይነት፡፡)ከዚህ በኋላ 500 ዘመን ቆይቶ ያንንም ያህል ትልቅ ሥራ ተደርገው ያልተቆጠሩ 4 ፊደላትን ጨመረ። የፊደላቱ ንድፍ እና ተመጣጣኝነት ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መጣ፡፡ ከልደት በፊት የመጀመሪያ መቶ ዓመት ላይ የመጀመሪያዎቹ ሦስት የሮማን ፊደላት ተሠሩ፤ ካፒታል ሌተርስ የሚባሉት ተጨመሩ፤ አጻጻፉም ከግራ ወደቀኝ ብቻ በመሆን ጸና፡፡
በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን በጽሑፍ መስመር ላይ ውበትን የሚጠብቁ ማሻሻያዎች ተደረጉለት (በቃላት መካከል ያለው ርቀት እኩል እንዲሆን ማድረጉን የመሰለው)
በ7ኛው መቶ ተነባቢነትን እና የጽሕፈት ፍጥነትን የሚጨምሩ ትናንሽ ፊደላትን መጨመሩን የመሰሉ ሥራዎች ተሠሩለት፡፡
በመካከለኛው ዘመን በፈረንሳይና ስፔይን ውስጥ የነበሩ የተለያዩ የአጻጻፍ ስልቶች ማስተማሪያዎች ብቅ አሉ፡፡
በሻር ለማኝ ጊዜ ዘ(768-814 እ.ኤ .አ የኖረ) የአልፋ ቤትን ደረጃ መደበኛና ቀዋሚ የሚያደርግ መንግሥታዊ ዓዋጀ ታወጀ፡፡ ሻር ለማኝ ራሱ ያልተማረ፣ ማንበብ እና መጻፍ የማይችል ቢሆንም መንግሥቱን አንድ ለማድረግ (አንድ) የጽሕፈት ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን የተረዳ (አስተዋይ) ነበር።
በዚኹም ምሑራኑን እና የሃይማኖት አስፋፊዎችንም አንድ አድርጐ፣ ሕዝብንም እንዲሁ ወደ አንድነት እሚያመጣ መሆኑን ስለተገነዘበ፣ ለዚሁ ሥራ የዮርኩን አልኩዊንን (አማካሪው የነበረ) በመመደብ ከተለያዩ ክልሎች የተለያዩ የአጻጻፍ ስልት አላባዎችን በመጠቀም፣ የካሮሊንጋን አጻጻፍ የተባለውን የሮማዊው ጽሕፈት ስልት እንዲያዝ አድርጓል፡፡
እስከ 13ኛው መቶ ክ/ዘ አንዳንድ ጊዜያዊ የአጻጻፍ ለውጦች በማድረግ፣ ጐቴክን የመሳሰሉ ድርብ ጽሑፎችን ጨማምሮ በ1500 ዛሬ ላይ አውሮፓውያን የሚጠቀሙበትን መልክ ያዘ፡፡
የጥናት ወረቀቱ የግእዙን ታሪክ ለመቀጠል፣ በግእዝና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ዩሮም እክልናዊነት ያለው ምሑራዊው አቀራረብ ያደረሰውን በደል ያነሳሳል፡” ይህ አውሮፓን ማዕከል ያደረገውን ምሁራዊነት፣ በዶክተር አየለ በከሬም ሰፊ እና ኃይለኛ ሙግት የተያዘበት ጉዳይ ነው፡፡
አየለ በከሬ በዩሮም እክልናዊ እውቀት ስለ ኢትዮጵያ፣ አልፎም ስለ አፍሪካ ታሪክ፣ በተለይም ከጽሕፈት ጋር የተያያዙ የታወቁ የ “ሂስትሪ” ትምሕርቶች እየጠቃቀሱ በመሞገት ከጣሉ በኋላ አፍሮምዕክልናን ያስይዛሉ፡፡
በጋብሬላ ኤፍ ሴልታ ወረቀትም የግእዝ ፊደላትን በተመለከተ የዩሮምዕክልናው ዘረኛ አመለካከት፣ የተሳሳተ እውቀትን ይዞ እንደሚኖር ተገልጿል፡፡
“የግእዝ ሥርዓተ ጽሕፈት ታሪክን እንደሮማዊው ለማቅረብ የቀለለ አይደለም። ለዚህም በዋነኝነት በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ፣ ነገር ግን ልክ ያልኾነ፣ በዩሮምዕክላዊው ግምቶች ላይ የተመሠረተው ትምሕርት ያመጣው ነው፡፡ ዛሬም የዩሮምእክልናዊው አመለካከት በስነ ቋንቋ አፈራረጅ ግዕዝን አፍሪካዊ ቋንቋ ሳይኾን ሴማዊ ቋንቋ ውስጥ ይመድበዋል፡፡ የግእዝን የትመጣ ጥናት ላይ የዘረኝነቱ ወረርሽኝ እንደሲልቪያ ፓንክረስት ባሉት የቅርብ ጊዜ ምሑራዊ የታሪክ ሥራዎች ላይም የሚታይ ነው፡፡”
ሲልቪያ ፓንኮርስት “ኢትዮፕያ ኤ ካልቸራል ሂስትሪ” በማለት ባቀረቡት መጽሐፍ ከደቡብ ዓረብያ የመጡ ፈላሲያን “የበለጠ ድንቅ የኾነ ሥልጣኔን” ለኢትዮጵያ እንዳስተዋወቁ ይገልጻሉ፡፡


Published in ጥበብ

“መድረክ መቅደስ ነው፤ ካህናቱም ተዋንያኑ” የሼክስፒር ዝነኛ አባባል
የዘወትር የክህነት ሥርአት አይታጐልም፤ ነውር ነው፤ ጫን ሲልም ሃጢያት ነው፡፡ ከህዝብ (ከተደራሲያን) የተለዩ (የተቀደሱ) ካህናት (ተዋንያን) የመለየታቸው ግብ እና ምስጢር በመቅደሱ ዘወትር እንዲያገለግሉ፣ ከእለት ተእለት የኑሮ ውጣ ውረድ ተለይተው ለመረጣቸው ህዝብ ዘወትር እንዲያጥኑ ነው፡፡ በሼክስፒር ሃሣብ ከተስማሙና “መድረክ መቅደስ ነው” ካሉ 24 ሠአት እንዲንተገተግ የታዘዘውን የመቅደሱን ፋና ዘወትር ሊለኩሱ፣ በብርሃኑ ድምቀት እና ሙቀት የመድረኩን ቅድስና ሊያውጁ ይገባል፡፡ ለእነዚህ ከአህዛብ (ተደራሲያን) የተለዩ (የተቀደሱ) ጠቢብ ሌዋውያን፤ መድረክ የሥራ ቦታቸው ብቻ ሣይሆን የመኖሪያ ቤታቸው፣ የማረፊያ ታዛቸው፣ የምግብ ገበታቸው በአጠቃላይ የእለት ከእለት ኑሮአቸው መሃከለኛ ጉዳያቸው ነው፡፡
ይህን ለማለት ያነሣሣኝ ባለፈው እሁድ በመዲናችን ስለተከናወነ አንድ ክስተት ጥቂት ልል ፈልጌ ነው፡፡ በእለቱ ከቀኑ 8፡00 ጥሪ ወደተደረገልኝ የመፅሃፍ ቅዱስ ታሪክ ፊልም ትርጉም ሥራ ምረቃ በአል ላይ ለመገኘት በ6 ኪሎ የስብሠባ ማዕከል ተገኝቻለሁ፡፡ ስነ ስርአቱ በመርሃ ግብሩ መሠረት የተከናወነ ቢሆንም አንድ ትልቅ ክፍተት ነበረበት። የሥራው ባለቤት ማለትም የፊልሙ ዋና ተርጓሚ እና ተራኪ በቦታው አልተገኘም፡፡ በስነስርዓቱ ማብቂያ ላይ የፕሮግራሙ መሪ ወደ መድረክ መጥተው፣ የስራው ባለቤት በስፍራው ያልተገኘው ከዘወትር ሥራው ከብሔራዊ ቲያትር መድረክ ሊለይ ባለመፍቀዱ እንደሆነ ገለፁ፡፡ በዚህ ተደንቀን ሣንጨርስ ሌላ የሚያስደንቅ ነገር ነገሩን፡፡ በእለቱ ተዋናዩ የቀለበስ ስነ ስርአቱን በብሄራዊ ቲያትር እንደሚፈፅም የገለፁት የመድረክ መሪው፤ ለፊልም ምርቃት የተገኘነው ታዳሚዎች በብሔራዊ ቲያትሩ ሠርግ (ቀለበት) ላይ እንድንታደም ግብዣ አቀረቡ፡፡
በቀጥታ ወደ ስፍራው አመራን፡፡ ትርኢቱ ገና ባለመጠናቀቁ ከትያትር ቤቱ ጀርባ ለአፍታ ተቀምጠን ሊፈፀም ጥቂት የቀረውንና በተስፋዬ ገ/ማርያም የተዘጋጀውን “ቶፓዝ” ቲያትር መመልከት ጀመርን። ቲያትሩን ከጀመሩት ተመልካቾች እኩል ውጥረት ውስጥ ስላልሆንን፣ የመድረኩን ዙሪያ ገባ በግርምት እያስተዋልን ነው፡፡ መድረኩ ያው መድረክ ነው፡፡ አበባ በታኝ ህፃናት፣ የሠርግ ፕሮቶኮል አልያም ሌላ ሠርግ ሠርግ የሚሸት ምንም አይነት ድባብ አይታይም፡፡ ወደ ፍፃሜው በተቃረበው የቲያትር ታሪክ ውጥረት ውስጥ ያለው ተመልካች፤ የመጨረሻ ትንፋሹን ሊተነፍስ ሣንባውን በአየር፣ ልቡን በትኩስ ደም ሞልቶ ጫን ጫን ይተነፍሣል፡፡ ቲያትሩ አለቀ። ታዳሚው ተነፈሠ፡፡ ለውብ ተውኔቱ እና ለድንቅ ተዋንያኑ ከመቀመጫው ተነስቶም አጨበጨበ። ወዲያውኑ ከአዳራሹ ጀርባ በድምፅ ማጉያ አንድ ሠው መናገር ጀመረ፡-
“ውድ ተመልካቾች፤ እባካችሁ ለ10 ደቂቃ ታገሱን” ህዝቡ ትንፋሹን ሠበሠበ፡፡ እንደቆመ ወደ መድረኩ በጉጉት አፈጠጠ፡፡ ተናጋሪው ቀጠለ፡-
“በእለቱ የተመለከታችሁት ተውኔት፣ መሪ ተዋናይ አርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፤ ይህ ተውኔት እየተካሔደ ባለበት ሠአት፣ ተዋናዩ ያዘጋጀው የመፅሃፍ ቅዱስ የዘፍጥረት ታሪክ የአማርኛ ትርጉም ትረካ ፊልም በመመረቅ ላይ ነበር። ነገር ግን እናንተን ተመልካቾቹን እና መድረኩን በማክበር በምረቃው ላይ ሣይገኝ ቀርቷል፡፡ ሌላ ጭብጨባ እና ፉጨት፡፡
በመቀጠልም አርቲስቱ ሊያስተላልፈው የሚፈልገው መልእክት እንዳለ ገልፆ እድሉን ለአርቲስቱ ሰጠ፡፡ በተውኔቱ ፍፃሜ ህዝቡን ለማመስገን እና ለመሠናበት ከተደረደሩት አንጋፋ እና ወጣት ተዋንያን መካከል ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፤ ወደፊት በመውጣት ለህዝቡ ያለውን ክብር በታላቅ ትህትና ከገለፀ በኋላ አንድ ነገር ለማከናወን ህዝቡን ፈቃድ ጠየቀ፡፡ በሚያከብረው መድረክ እና በሚወደው ህዝብ ፊት ማግባት ቀለበት ማሠር እንደሚፈልግ…
ረጅም ዝምታ … ግራ መጋባት … በስተመጨረሻ ታላቅ ፉጨት እና ጭብጨባ አዳራሹን አናወጠው። አርቲስቱ ተንበርክኮ ወደ መድረኩ ለወጣችው ባለቤቱ፣ ከተወዳጇ አርቱስት ሃረገወይን አሠፋ የተቀበለውን ቀለበት አጠለቀ፡፡ መድረኩ ተናወጠ። በስተመጨረሻ አርቲስቱ ለተወሠኑ ታዳሚዎቹ ያዘጋጀው የእራት ግብዣ፣ በራስ ሆቴል እንዳለ እና የሙሽሮቹ ማረፊያም ታላቁ የነፃነት አባት ኔልሠን ማንዴላ ከአመታት በፊት ባረፉበት ታሪካዊ ክፍል እንደሆነ ሲናገር ሌላ አድናቆት እና ጭብጨባ አስተጋባ፡፡ ከእራት ግብዣው በኋላ ማንዴላ አርፈውበት ከነበረበት ክፍል ፊት ለፊት ከፎቶግራፋቸው ጐን ቆሜአለሁ፡፡ አርቲስቱ እና ባለቤቱ በአፍሪካውያን ልብስ ደምቀው ያረፉበትን ታሪካዊ ክፍል ለታዳሚዎቻቸው ኩራት ማስጐብኘት ጀመሩ፡፡ ከህዝብ ሁካታ እና ጫጫታ አይሎ የሚሠማ የገዛ እራሴን ድምጽ እያደመጥኩ በሃሳብ ተውጫለሁ፡፡ አርቲስቱ ምን እያደረገ ነው? ለአፍታ በሃሳቤ የኋሊት ገሠገስኩ፡፡ ከመድረክ እና ከጥበብ ጋር የተቆራኙት የአርቲስቱ አብይ የህይወት ክስተቶች በየተራ ታወሱኝ፡፡
አርቲስቱ በሚወዳቸው እና በሚጠራባቸው እናቱ ቀብር ዕለት በሚወደው መድረክ እና በሚያከብረው ህዝብ ፊት በስራ ላይ ነበር፡፡
የመጀመሪያ ልጁን አንደኛ አመት ያከበረው “ፊልም ቦይ” የተሰኘ መጽሐፉን ለልጁ በስጦታ በማበርከት ነው፡፡
በአንድ ወቅት ልደቱን ያከበረው ከጐዳና ልጆች ጋር ድሪቶ ለብሶ ለሚሠራው Experimental ቲያትር እየተዘጋጀ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ነበር በቅርቡ በዚሁ ጋዜጣ “The show must goon” (ትያትር አይቋረጥም) በሚል ርእስ የፃፈው ጽሑፉ የታወሰኝ። በዚህ ጽሑፍ አርቲስቱ ለመድረክ እና ለሙያው ሊሰጥ ስለሚገባ ክብር ጠንከር ባሉ ቃላት ተግሣፅ አዘል መልእክት ማስተላለፉ ሲታወሰኝ በብእር ያወጀውን በግብር እያሳየ እንደሆነ ተገነዘብኩ፡፡
ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፤ ዘርፈ ብዙ አርቲስት ነው፡፡ እጅግ የበዙት ሙያዎቹ ከመድረክ እና ከስክሪን ተርፈው የግሌ በሚለው የእለት ተእለት ህይወቱ ሠርገው ከመግባት አልፈው የየእለት እንቅስቃሴው አካላት ሆነው ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህም ነው በአንድ ወቅት በዚሁ ጋዜጣ “ሮማንቲሲዝም” በሚል ርእስ በፃፈው ጽሑፍ እንደገለፃቸው፣ የሮማንቲክ ገጣሚያት ባይረን እና ሼሊ በተራ የህይወት እንቅስቃሴው ጭምር የህይወት ፍልስፍናውን በመግለጽ ሥራ ላይ የተጠመደው፡፡  
ፈለቀ የመድረክ መሪ፣ ተዋናይ፣ ገጣሚ፣ ተራኪ እና አዘጋጅ ነው፡፡ በእነዚህ ሙያዎቹ ምስጉን እና በብዙዎቹም በአገር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ነው፡፡ በተለይ ከሚታወስባቸው ሥራዎቹ መካከል፡-
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ በ4 ቀን ውስጥ ያዘጋጀው ኦፔራ Experimental play
በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተሠራውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ፊልም ትረካ ከአንጋፋ ተዋንያኑ ፈቃዱ ተክለ ማርያም እና መሠረት መብራቴ ጋር
በ1941 ዓ.ም የታተመውን የተመስገን ገብሬን (የአገራችንን የመጀመሪያ አጭር ልብ ወለድ) “የጉለሌው ሠካራም” ትረካ
በቡርኪናፋሶ የፊልም ፌስቲቫል የተሸለመበት እና በክርስቶስ ሣምራ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የሠራው In search of the Devil ፊልም … ከብዙ ሥራዎቹ መካከል እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ፈለቀ ሌላው የሚለይበት ባህሪው በየጊዜው ያገኛቸውን ሽልማቶች በማህበረሰብ ግንባታ ሒደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል ብሎ ላመነባቸው አርአያ ግለሰቦች መታሠቢያነት ማበርከቱ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-
በጥቅምት 2003 ዓ.ም ያገኘውን የ“ቤስት ፊልም አክተር” ሽልማት በፊልም ስራ ለሚሠማሩ ኢትዮጵያውያን
በ2004 ያገኘውን የ“ምርጥ የመድረክ ተዋናይ” ሽልማት በሙያው ለተሠማሩ አንጋፋ ከያንያን
በ2006 ያገኘውን የ“ምርጥ ፊልም ተዋናይ” ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፊልም ላሣዩት አጤ ምኒልክ እንዲሁም
በኦርማኖ አልሚን ፊልም በትረካ፣ በተርጓሚነት እና አዘጋጅነት ከተበረከቱለት ሽልማቶች ሁለቱን ለብሔራዊ ቲያትር እና ለኔልሰን ማንዴላ ቀብር ሥነ ሥርአት መታሰቢያነት አበርክቷል፡፡
የዚህ  ጽሑፍ አላማ አርቲስቱን በደረቁ ማሞካሸት አይደለም፡፡ በዚህ የጥድፊያ እና የ“ከተፋ” ዘመን ለሙያ መኖር እና ሙያን መኖር እንደሚቻል ከዚህ ወጣት ከያኒ እንድንማር በማሰብ ነው፡፡
በመግቢያዬ ላይ እንደተባባልነው ሁሉም ሰው የተቀበለው የኔ የሚለው መክሊት አለው፡፡ የሰርክ መስዋእቱን የሚያቀርብበት የራሱ መሠዊያ ባለቤትም ነው፡፡ ለተለየለት ሙያም ቅዱስ አገልጋይ ሌዋዊ ነው፡፡
የስራ ቦታ ቢሮ ብቻ አይደለም፤ ሥራ ህይወት ነው፤ ህይወትም ሥራ ነው፡፡ እንደማይቋረጠው የክህነት ሥራ ሁሉ የተጐናፀፍነውን የክህነት ካባ ቢሮ ሠቅለን አንውጣ፡፡ የትም ለብሰነው በኩራት እንንጐማለል፡፡ ሥራችንን እንኑረው-እንደ ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፡፡  
The show must go on! ትርኢት አይቋረጥም!

Published in ጥበብ

የቀድሞው የፓርላማ አባል “የተከበሩ አቶ ተመስገን ዘውዴ ህይወትና የፖለቲካ ቁጭት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን መፅሀፍ የፃፈው አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በመፃፍ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ቀደም “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ” የተሰኘ በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የህይወትና ፖለቲካ ጉዞ ላይ ያተኮረ መፅሀፍ መፃፉ ይታወሳል፡፡
የአሁኑ መፅሃፍም ከተከበሩ አቶ ተመስገን የትውልድ መንደር ጀምሮ ስለ ትምህርትና ፖለቲካ ጉዟቸው፣ ስለ ግንቦት ሰባት ምርጫና ስለ ፓርላማ ባልንጀሮቻቸው እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ታሪኮችን ያስቃኛል፡፡ 276 ገፆች ያሉት መፅሀፉ፤ በ27 ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን በ55 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡

“The Magic of thinking big” በሚል በዶክተር ዴቪድ ሺዋርትዝ የተፃፈው መፅሀፍ በጋዜጠኛ ሱራፌል ግርማ “በትልቁ የማሰብ ሀይል” በሚል ተተርጉሞ በያዝነው ሳምንት ለንባብ በቅቷል፡፡ 176 ገፆች ያሉት መፅሀፉ፣ እንዴት ከፍ አድርጐ ማሰብ እንደሚቻል፣ ታላቅ አስተሳሰብ በማንኛውም መንገድ አዋጭ ስለመሆኑ፣ ሰዎች ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ሲያምኑ እንደሚሳካለቸው እና በአጠቃላይ ትልቅ አስተሳሰብ ወደየትኛውም የስኬት መንገድ ሊወስድ እንደሚችል የሚተነትን ነው፡፡ “በትልቁ የማሰብ ሀይል” በብር 40.50 እየተሸጠ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል  “The power of positive Living” በሚል በዶክተር ኖርማን ቪንሰንት ፒል የተፃፈውና “የስኬት ምስጢር” በሚል ወደ አማርኛ የተተረጐመው መፅሀፍም ሰሞኑን  አንባብያን እጅ ደርሷል፡፡ በፋሲካ ግዛው የተተረጐመው መፅሀፉ፣ እንዴት አሸናፊ መሆን እንደሚቻል፣ ሀብትን ሳያባክኑ ስለመጠቀም፣ ለስኬት የማያወለውል ቆራጥነት አስፈላጊ ስለመሆኑ፣ መከራን ወደ ጥቅም እንዴት መለወጥ እንደሚቻልና በመሰል የስኬት ምስጢሮች ዙሪያ ሰፊ ትንታኔን ይዟል፡፡ 176 ገፆች ያሉት መፅሀፉ፣ በ40 ብር ከ50 ሳንቲም በሁሉም መፅሀፍት መደብሮች እየተሸጠ ይገኛል፡፡

“The Five Love Languages” በሚል በጋሪ ቻፕማን የተፃፈው መፅሀፍ “አምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች” በሚል በቢኒያም አለማየሁ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ሰሞኑን ለአንባቢያን ቀረበ፡፡
በ172 ገፆች የተቀነበበውና በ14 ምዕራፎች የተከፋፈለው መፅሀፉ፣ የመቀበልና የማድነቅ አባባሎች፣ የፍቅርና ስጦታ፣ ፍቅረኛን ማገልገል፣ ጥሩ የፍቅር ጊዜ እና አካላዊ ንክኪ በማለት አምስቱን የፍቅር ቋንቋዎች በመግለፅ በስፋት ያብራራል፡፡ መፅሃፉ በ35 ብር ከ50 ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡   

“የሸገር ወጐች” ለአምስተኛ ጊዜ ታተመ
የገጣሚ ታየች ወልደማርያምን የግጥም ስብስቦች የያዘው “ልትፋው ብዕሬን” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን ለንባብ የቀረበ ሲሆን ነገ ከጠዋቱ 3 ሰዓት በሐገር ፍቅር ቲያትር ቤት ይመረቃል ተብሏል፡፡ በ108 ገፆች የተቀነበበው መፅሃፉ፤ በ30 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩል በጋዜጠኛ ሰለሞን ታደሰ የተፃፈው “የሸገር ወጐች” መፅሀፍ ለአምስተኛ ጊዜ ታትሞ ለንባብ ቀረበ፡፡ መፅሀፉ ስለ ድብቅ የራቁት ጭፈራ ቤቶች፣ ስለ ከተማችን ሀብታሞች ገመና፣ ስለ ሚስጢራዊ ማሳጅ ቤቶች እና ከአለማችን ትልልቅ ከተሞች አንዷ ስለሆነችው ዱባይ ሁለት ገፅታዎች ያስቃኛል፡፡ ወጐችና እውነተኛ ታሪኮች የተካተቱበት መፅሀፉ፤ በብር 39.50 ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “ቦሌ ፒኮክ ጋ ጠብቂኝ” የተሰኘ መፅሃፍ ማሳተሙ ይታወሳል፡፡

በግርማ ባልቻ ተፅፎ የተዘጋጀውና “ናይልና ግብፅ ኢኮኖሚያዊ ይዞታ፤ ከትላንት እስከ ዛሬ” የተሰኘው መፅሀፍ ባለፈው ሳምንት ለንባብ በቃ፡፡ በ138 ገፆች የተዘጋጀው መፅሀፉ፤ በናይልና በግብፅ  አጠቃላይ ውዝግቦችና አሁን ግብፅና ኢትዮጵያ በወንዙ ዙሪያ ስላላቸው ግንኙነቶች እንዲሁም የአባይንና የግብፅን ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና ተያያዥ ጉዳዮችን ያስቃኛል፡፡ መፅሀፉ በ42 ብር ለገበያ መቅረቡም ታውቋል፡፡

Monday, 23 December 2013 09:58

እቴጌ ጠየቁ

አዲስ ሐሳብ አፈለቁ ሳይደብቁ
        የኔ ምኒልክ ይስሙኝ
        ይህን ውብ ቦታ አገር ስጡኝ
        ቤት ልሥራ ጌታዬ ባፋጣኝ
        ይህችን አዲስ አደይ አበባ አዩልኝ
    የፍንፍኔ ውበት አይሎ
    የጣይቱስ ያገር ጥያቄ መች ተዘሎ
ሕይወት አገር አበባ
በፍል ውኃ ዳርቻ ተገነባ
ይህች አደይ አበባ
ስመ ውልደቷ በዓለም ዙሪያ አስተጋባ
የእኛይቱ ውብ አዲስ አበባ
እንሆ የኔ ውብ ጣይቱ
ቤት ሥሪና ያንቺ ትሁን አገሪቱ
በማለት
    ምኒልክ ለጣይቱ መረቋት
    በፍቅር ቃለ አንደበት ለገሷት
ይኸው የምኒልክ በረከት
የጣይቱ ልብ ምርኮ መሠረት
ሕዝብ ከቶባት ሕዝብ ገንብቷት
    የአፍሪከ አንድነት መዲና አለኝታ
    የዓለም ሰላም መድረክ መከታ
    የአገር ኤኮኖሚ የአገር ፖለቲካ ዋልታ
    እናት አዲስ አበባ ውብ አገር ውብ ስጦታ
ገ.ክ.ኃ




Published in የግጥም ጥግ

በሰዓሊ ስዩም አያሌው የተሳሉ 27 ስዕሎች የተካተቱበትና “ጥልቅ ስሜትና እውነታ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የስዕል ኤግዚቢሽን፤ ባለፈው ሳምንት  በጋለሪ ቶሞካ የተከፈተ ሲሆን ለአንድ ወር ተኩል ለተመልካች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ የስዕል ኤግዚቢሽኑ፤ በዋናነት በዝቅተኛው የህብረተሰቡ እውነታዎች ላይ እንደሚያተኩር የጠቆሙት ሰዓሊው፤ በተለይም ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ እና ከኑሮ ዘይቤ ለውጥ ጋር እየጠፉና እየቀሩ የመጡት የጠጅ፣ የጠላና የአረቄ ቤቶች ማህበራዊ ግንኙነቶች ይንፀባረቁበታል ብለዋል፡፡

Page 5 of 16