ጋለሪያ ቶሞካ በትላንትናው እለት “ግልፅና ድብቅ ከብርድልብስ ስር” በሚል ርዕስ ለሁለት ወራት የሚቆይ የስዕል አውደ ርዕይ ከፍቷል፡፡ ለአውደ ርዕይ የቀረቡት የሰዓሊ ዘላለም ግዛው የስዕል ስራዎች ሲሆኑ ብዛታቸው 30 ነው፡፡ ሥዕሎቹ በማህበራዊ ህይወት ላይ የሚያተኩሩ እንደሆኑና በብርድልብስ የተሸፈኑ  ግለሰባዊ የውስጥና የውጭ ችግሮችን አጉልተው እንደሚያሳዩ ሰዓሊው ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
ሰዓሊ ዘላለም ግዛው፤ በ1990 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “አለ ፈለገ ሰላም የስነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት” ዲፕሎማ እንዲሁም በ2003 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኘ ሲሆን ከ20 ጊዜ በላይ በአገር ውስጥ አንድ ጊዜ ደግሞ በአየርላንድ ከሌሎች ሰዓሊዎች ጋር ስራዎቹን ለእይታ አብቅቷል፡፡ በግሉ  አውደ ርዕይ ሲያቀርብ የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዶ/ር ወሮታው በዛብህ የተዘጋጀውና ከ70 የሚበልጡ ሥራ ፈጣሪዎችን ታሪክ የሚያስቃኘው “ለራስ ማን እንደራስ” የተሰኘ መጽሀፍ ሰሞኑን ለንባብ የበቃ ሲሆን የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በአምባ ሆቴል ይመረቃል፡፡ መፅሀፉ በራስ ፈጠራ እንዴት መለወጥ እንደሚቻልና በመፅሀፉ የተካተቱ ከ70 በላይ ሰዎች እንዴት እንደተለወጡ የተርካል ተብሏል፡፡ በምረቃው ዕለት የጂኒየስ ማሰልጠኛ ተቋም ሰልጣኞች ምረቃ፣ የስኬታማ ሰዎች ልምድና ሌሎች ፕሮግራሞች እንደሚካሄዱ ተጠቁሟል፡፡ መፅሀፉ በ60 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን የመፅሀፉ አዘጋጅ በሥራ ፈጠራና ብልፅግና ዙሪያ በርካታ መፃህፍትን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወቃል፡፡

በይታገስ ጌትነት ገበየሁ የተፃፉ አጭር ልቦለዶችን የያዘ “የደመና መንገድ” የተሰኘ መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ አጫጭር ልብወለዶቹ በተለያዩ ማህበራዊ፣ አገራዊና የፍቅር ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናሉ ተብሏል፡፡ በ124 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ በ35 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡  ደራሲው ከዚህ ቀደም “ጥቁር ነጥብ” እና “ደጅ ያደረ ልብ” የተሰኙ መፅሀፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡

ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ይከፈታል፡፡ ፌስቲቫሉ እስከ ህዳር 14 የሚቆይ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመረጡ ፊልሞች እንደሚቀርቡ የፌስቲቫሉ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ በብሄራዊ ቴአትር የሚከፈተው ፌስቲቫሉ፤ በጣሊያን የባህል ተቋም፣ በአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴስና በሩሲያ የባህል ማዕከል ከተካሄደ በኋላ የመዝጊያ ፕሮግራም በሂልተን ሆቴል እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡ የዘንድሮው የፊልም ፊስቲቫል “Children Film World፡ Colour or Black and White” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን “አዲሱ ትውልድ ከፊልም አኳያ ያለው ምልከታ” በሚል ርዕስ ውይይት እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፌስቲቫሉ ወቅት ተሰጥኦ ባላቸው ወጣቶች የተሰሩና ከመላው ዓለም የተውጣጡ ፊልሞች መረጣ የሚካሄድ ሲሆን የልጆች ልዩ ፕሮግራም እንደሚኖርም ተጠቁሟል፡፡
ከስዊድን በመጣ የፊልም ባለሙያ የፊልም ስልጠና እንደሚሰጥ የገለፁት  አዘጋጆቹ፤ ከህንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበርም ለተመረጡ ሁለት የህንድ ፊልሞች የአማርኛ ሰብታይትል ይሰራል ብለዋል፡፡ የፊልም አፍቃሪያን በዘጠነኛው አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ላይ እንዲታደሙ ግብዣ ቀርቦላቸዋል፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ 16 የኢትዮጵያ ፊልሞች የሚሳተፉ ሲሆን ከነዚህ መካከል “ረቡኒ” “የመሃን ምጥ” ወ/ሪት ድንግል፣ “በጭስ ተደብቄ”፣ ከህግ በላይ፣ ነቄ ትውልድ፣ ኤሽታኦል፣ ታሽጓል እና ሌሎችም ተካተዋል፡፡

በወጣቱ ገጣሚ አያሌው እውነቴ የተጻፈውና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ከ65 በላይ ግጥሞችን የያዘው “ቁምታም ጾም”  የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሃፍ፣ ከትናንት ጀምሮ በገበያ ላይ መዋሉን ገጣሚው ለአዲስ አድማስ ገለጸ፡፡
92 ገጾች ያሉት “ቁምታም ጾም” የግጥም ስብስብ መጽሃፍ፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚገኙ የመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች በ42.50 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ለውጭ አገራት የመሸጫ ዋጋው 9 የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡
መጽሃፉ በቅርቡ በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር እና በደብረ ማርቆስ በሚካሄዱ የስነ-ጥበብ ዝግጅቶች በይፋ እንደሚመረቅ የገለጸው ገጣሚው፣ በቀጣይም ለህትመት የተዘጋጁ ሌሎች የግጥምና የወግ ስብስብ ስራዎችን ለአንባብያን እንደሚያበቃ ገልጧል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጽሁፍ ተማሪ በነበረበት ወቅት፣ በዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል የተለያዩ የስነ-ጽሁፍ ስራዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ገጣሚው፣ ከ17 አመታት በፊትም ለህትመት የመጀመሪያ ስራው የሆነውን “የበረከቱ አስኳል” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሃፍ ለንባብ አብቅቷል፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 15 November 2014 11:29

ይንጋ ብቻ!

 “ሰሞኑን ይፈርሳል እየተባለ ነው .. ሌላ ቤት እንደመፈለግ አገር ቤት ልሂድ ትላለህ?” አሉኝ እትዬ አልማዝ፡፡  “ዝም ብለው የተወራውንማ አይስሙ፡፡ ይፈርሳል ተብሎ ከተወራ ስንት ጊዜ ሆነው እትዬ.. ለነገሩ ከአንድ ሳምንት በላይ አልቆይም..” አልኳቸው
ለመጓዝ እንደተነሳሁ ስላወቁ ነው መሰል፡-
“ብቻ አልማዝ አልነገረችኝም እንዳትል?” ብለውኝ ከቤት አከራዬ ከእትዬ አልማዝ ጋር ተለያየን፡፡ እንደተለመደው መስቀልን ከቤተሰቦቼ ጋር ለማሳለፍ ወደ ሀገር ቤት ተጓዝሁ፡፡ የመስቀልን በዓል ስናከብር፣ ዘመድ አዝማድ ስንጠያይቅ .. የእንጀራ ጉዳይ ብዙ ካራራቀን አብሮ አደጎቼ ጋር ‹እንዴት ነህ!› ስንባባል ቀኑ ክንፍ አውጥቶ ይበር ጀመር፡፡ ለሳምንት ያልኩት ሰውዬ ሦስት ሳምንት ሰነበትኩ፡፡ ስመለስ የተከራየኋት ጎጃም በረንዳ ያለችው ቤቴ የለችም፡፡ ቤቴ ብቻ ሳትሆን ሰፈሩ በሙሉ የለም፡፡ በምትኩ በዶዘር የታረሰ መሬት ጠበቀኝ፡፡ አከራዬ እትዬ አልማዝስ? አድራሻቸውን ማጠያየቅ ጀመርኩ፡፡ የእትዬ አልማዝ አበልጅ ቤት አልፈረሰም፡፡ ከመንገድ ወደ ውስጥ ገባ ያለ ስለሆነ አልተነካም፡፡ አበልጅየውን ከቤቷ በር ላይ አገኘኋት፡፡ ገና እንዳየችኝ፤
“ዕቃህ ከኔ ዘንድ ተቀምጧል፤ በል ከመጣህ ውሰድልኝ” አለችኝ
“ገና ከመንገድ እየገባሁ‘ኮ ነው… ከነሻንጣዬ እያየሽኝ? ባይሆን ነገ ተነገወዲያ ቤት ፈልጌ ልከራይና እወስደዋለሁ”
“እንግዲያውስ እስክትወስድ ድረስ በየቀኑ ሃያ ብር ትከፍላለህ!”
“አልጋና ፍራሽ እኮ… ሌላ ዕቃ የለኝም… ለዚህ ነው ሃያ ብር በየቀኑ?”
“ካልፈለግህ አሁኑኑ አውጣልኝ! አልጋና ፍራሽ ቢሆንስ? እንኳን ያንተ ተጨምሮ ሆሆ …”
“እሺ …. እሺ እከፍላለሁ” አልኳትና ከአጠገቧ ዘወር አልኩ፡፡
ሥራዬ አየር ባየር ንግድ ነው፡፡ ከመርካቶ ነጋዴ ዕቃ በዱቤ እወስድና ቀኑን ሙሉ ሳጣራ እውላለሁ፡፡ ስጨርስ ዋናውን ለነጋዴው እመልስለትና ትርፉን እወስዳለሁ፡፡ በነጋታውም እንደዚያው አንዳንዴ አሪፍ ጥቅም ይገኛል፡፡ አንዳንዴ ጥቂት ቢሆንም ለክፉ አይሰጥም፡፡ የሚከፋው መንገድ ላይ ስንጮህ ደንብ አስከባሪ ይዞን ከተወረሰብን ነው፡፡
ዓመት ሙሉ ያጠራቀምኩትን አገር ቤት ከቤተዘመድ ጋር ተካፍዬ መጥቻለሁ .. እጄ ላይ ያለው እንኳን ለቤት ኪራይና ከሁለት ቀን በላይ ውሎ አያሳድርም፡፡ አልጋ መከራየት ነው ያለብኝ፡፡ የት እንደምሄድ ደግሞ የኖርኩበት ነውና አውቀዋለሁ፡፡ አመሻሽ ላይ በበቆሎ ተራ በኩል በጃሊያ፣ አልጋ ተራ፣ ጌሾ ግቢ ወይም በሶማሌ ተራ በኩል ወደ አሜሪካ ግቢ የሚመጣ ሰው፤
“አልጋ አለ … ክፍል ለብቻ! … ፍራሽ ፈላጊ … መኝታ አለ!” የሚል ጥሪ እስከ እኩለ ሌሊት ሲሰማ ያመሻል፡፡ አሁን አሁን አልሰማም እንጂ በፊት “ኬሻ በጠረባ፣ ሻዋር በባልዲ! … መኝታ አለ… መኝታ ፈላጊ” የሚል ጥሪም ይሰማ ነበር፡፡
አመሻሽ ላይ በበቆሎ ተራ በኩል ወደ አሜሪካ ግቢ አመራሁ … ጉራንጉር ለጉራንጉር ከተጠማዘዝኩ በኋላ ይሻላል ያልኩትን መኝታ ለአንድ ቀን በአርባ ብር ተከራየሁ፡፡ አጀብ! የሶስት ብር አልጋ አርባ ብር!
ስራ ከጀመርኩ ገና አምስት ቀኔ ነው፡፡ ከሃገር ቤት ከመጣሁ በኋላ ሥራ አልነበረም፡፡ ሁሌም ይኸው ነው፤ ጥቅምት እስኪጋመስ ገበያው ቀዝቃዛ ነው፡፡ ይሄ ሳያንስ አንዱ ደንብ አስከባሪ እቃዬን ወስዶብኝ በስንት ልምምጥና በስንት ልመና ነው የለቀቀልኝ፡፡ ያውም የሻይ ላስጨብጠው ቃል ገብቼ፡፡ ምን ይደረግ? ደሞ‘ኮ የሚገርመው “እዚያ ከወሰድኩህ የምትቀጣው ይኸን ያህል ነው፤ ስለዚህ ለኔ ግማሹን ልቀቅ” ማለቱ ነው፤ አይኑን አፍጥጦ፡፡ ትንሽም አያፍርም እኮ፡፡ ሌሎች ደግሞ አሉ፤ ኮስታራዎች፡፡ ያልተፈቀደ ቦታ ስትሸጥ ካገኙህ .. በቀጥታ ወደ ህግ ቦታ ይዘውህ የሚሄዱ፡፡ በአንድ ፊቱ የነሱ ይሻላል፡፡ ይኸኛው ግን የለመደ ነው፡፡ ቀን እየጠበቀ አምጣ ይላል፡፡ አምጣ … አምጣ … ማቆሚያ የለውም፡፡
ከተከራየሁት አልጋ ላይ ጋደም ብዬ የቀን ውሎዬን ሳሰላስል፣ በኮርኒሱ ውስጥ የሚሯሯጡ አይጦች ከሀሳቤ አናጠቡኝ፡፡
“አሁንስ አበዙት” አልኩ ለራሴ ብቻ በሚሰማ ድምፅ፡፡
“ምኖቹ?” አለኝ የፋይዚት ግድግዳ ከሚለየን ክፍል ያለው ተከራይ፡፡
“እህ .. ዐይጦች ሲንጎዳጎዱ አትሰማም?”
“ጣሪያው ላይ ድመቶቹ ሲሯሯጡስ አልሰማህም?” አለኝ፡፡
“ይገርማል! ጣራ ላይ ድመት ኮርኒስ ውስጥ አይጥ!”
“አይገርምም! አይጥና ድመት ግንባር ፈጥረው ሲረብሹን?”
“አይጥ ድመትን መፍራት አቆመ እንዴ?”
“አሊያም ድመት ንቀቱን አብዝቶ ይሆናል!”
“እንዲያ ነው እንጂ!”
ሁለታችንም በያለንበት ስንስቅ ቆየንና፡፡
“አንድ ወግ ልንገርህ… ” አለኝ ጎረቤቴ
“በጄ! ….” አልኩና ጆሮዬን ቀሰርኩ፡፡
“ገበሬው ሁላ ማልዶ ተነስቶ በሬዎቹን ጠምዶ ሲያርስ በሚውልበት አፍላ የእርሻ ወቅት ላይ አንድ ሳተና ገበሬ ሞፈር ቀንበሩን ተሸክሞ በሬዎቹን እየነዳ ወደ እርሻው ይሄዳል፡፡ አንደኛው ገበሬ ደግሞ ከቤቱ ታዛ ሥር ቁጭ ብሎ እንቅልፍ ያዳፋዋል፡፡ እንደሱ ብርቱ የነበረ ገበሬ ያለ ነገር በዚህ ቀን እንዲህ አይሆንም” በማለት አጠገቡ ሲደርስ፤
“ምን ሁነሃል… ስትጠጣ አደርክ?” ይለዋል
“እሱማ ቢሆን ምን ገዶ”
“ዛዲያ እርሻ እንደመውረድ ዕንቅልፍ የሚያዳፋህ በምን ምህኛት ነው?”
“አታምጣው ነው አንተው! … እንዲያው አንተዬ የአይጥ መንጋ ቲሯሯጥብኝ ላንዲት አፍታ ቅንድቤን ታልገጥም ነጋ!”
“ኧረግ ሞኝነት! አሁን እንዲያው ድመት አጣህ?”
“እሱ መች ጠፋኝ ብለህ… ተዲመትም ዲመት ያውም የተራበቺቱን ነው ያመጣሁ”
“ዛዲያ ምን ሆነች?”
“እሷማ ምን ትሆናለች! የድካሜን ጣመን ልወጣ ተመደቤ ላይ ጋደም እንዳለሁ ሳዳምጥልህ .. ድምጥ ቲጠፋ ጊዜ እንዲያው ይቺ ጎበዝ ዲመት ረፈረፈችልኝ አልኩና .. ኩራዜን አብርቼ እኸድልሃለሁ ዲመቲቷ ሆዬ … ተንጋላ ተኝታ ታጠባልሃለች!”
“ምን ታጠባለች በል!”
“አይጥ”
“ሃዬ በል! … የዘንድሮ ድመት አይጥ ታጠባ ጀመር!” እኔና ጎረቤቴ ተሳሳቅን፡፡
“በል እንቅልፌ መጥቷል … ደህና እደር!” አለኝ ጎረቤቴ፡፡
“ደህና እደር” ብዬው የሀሳብ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡
የድመት ተፈጥሮ አይጥን ማጥፋት አልነበር?
ቆይ … ቆይማ .. አሁን ለምሳሌ ያ ደምብ አስከባሪ፤ ተግባሩ ደንብ ማስከበር ሆኖ ሳለ፣ የተሰጠውን አደራ ዘንግቶ “የሻይ አምጣ” ሲለኝ … ድመቷ አይጥ አጠባች ማለት አይደል!
ሕዝብን እንዲያስተዳድር ኃላፊነት የተሰጠው ባለስልጣን፤ ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ተግባሩ ሆኖ ሳለ … የራሱን ጥቅም በማስቀደም ኪራይ ሰብሳቢ ሲሆን … ድመቷ ዐይጥ አጠባች ማለት አይደል!
ቆይማ … የድመቷ ወተት ቢነጥፍ … በድመት ወተት የጠገበ ዐይጥ ሁላ ምን ሊበጀው ነው?
ደንብ አስከባሪው “ለሻይ አምጣ”፣ ሲለኝ እሺ በማለቴ .. ድመቷ ዐይጥ እንድታጠባ ፈቀድኩ ተባበርኩ ማለት አይደለም? ይኸማ መሆን የለበትም! ከራስ መጀመር ጥሩ ነው …  ነገ የማደርገውን እኔ አውቃለሁ .. ለማንኛውም … ይንጋ ብቻ!

Published in ጥበብ
Saturday, 15 November 2014 11:28

የፀሃፍት ጥግ

እችላለሁም አልችልምም ብለህ ብታስብ አልተሳሳትክም፡፡
ሔነሪ ፎርድ
ወንድ ሆኜ ብወለድ ኖሮ አውሮፓን አስገብራት ነበር፡፡
ሜሪ ባሽኪርትሴፍ
(ሩሲያዊ ሰዓሊ፤ ስለ ጥበብ ሥራዋ የተናገረችው)
ሥራ በቅጡ እንዲከወን ከፈለግህ፣ ባተሌ ሰው ምረጥ፤ ሌሎቹ ጊዜ የላቸውም፡፡
ኢልበርት ሁባርድ
ዕድል የምታግዘው ለዝግጁ አዕምሮ ብቻ ነው፡፡
ሉዊስ ፓስተር
ከራሴ ግራ መጋባት ውጭ ለማንም ሰው የማበረክተው ነገር አልነበረኝም፡፡
ጃክ ኬሮአክ
ኤክስፐርት ማለት ማሰብ ያቆመ ሰው ነው፡፡ ለምን ያስባል? ኤክስፐርት ነዋ!
ፍራንክ ሊሎይድ ራይት
የምጠጣበት ብርጭቆ ትልቅ አይደለም፤ ግን ቢያንስ የራሴ ነው፡፡
አልፍሬድ ደ ሙሴ
ሰዎች ስለ ሥነጥበብ እኔ የማውቀውን ያህል ብቻ እንኳን ቢያውቁ፣ ሥዕሎቼን ፈጽሞ አይገዙኝም ነበር፡፡
ኤድዊን ሄንሪ ላንድሲር
ተሰጥኦ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ነው፡፡ ስለኤሌክትሪክ ነገረ - ሥራ አይገባንም፤ ግን እንጠቀምበታለን፡፡
ማያ አንጄሉ
ለንግድ ሥራ ተሰጥኦ አለኝ፡፡ ይሄን ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ልትማረው አትችልም፡፡
አላን ሹገር

Published in ጥበብ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የተስፋ ጭላንጭል አለው፡፡ ዛሬ ከሜዳው ውጭ በአልጀርስ ከአልጄርያ ጋር  እንዲሁም የፊታችን ረቡእ በአዲስ አበባ ከማላዊ አቻዎቹ ጋር በሚያደርጋቸው የ5ኛ እና 6ኛ ዙር  የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ከባድ ፈተና ይገጥመዋል፡፡ ዋልያዎቹ ለሁለቱ ጨዋታዎች የሁለት ሳምንት ዝግጅት ነበራቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት በቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አሰልጣኝ በነበሩት ሚቾ ከሚመራው የኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርገው 3ለ0 መሸነፋቸው አይዘነጋም፡፡   
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዓመት በፊት በነበረው ስኬታማ ጉዞ ዘንድሮ መቀጠል አለመቻሉ የሚያሳስብ ሆኗል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በቅድመ ማጣርያ ፉክክር ብቻ በ2013 እኤአ ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ መሳተፍ የቻለ ነበር፡፡ በዚህ ውጤቱ በውድድሩ የምድብ ማጣርያ በቀጥታ መሳተፍ ቢችልም ፉክክሩ  ከብዶታል፡፡  በተለይም በፌደሬሽኑ ዙርያ ያሉ አስተዳደራዊ ድክመቶች፤ የበጀት መራቆት፤ በትጥቅ እና ሌሎች ቁሳቁሶች አለመሟላት፤ በጡረታ በጉዳት እና በቅጣት የስብስቡ መመናመን፤ በማበረታቻዎች ማነስ  ዋና አሰልጣኙ ማርያኖ ባሬቶ በገጠሟቸው የስራ ውጣውረዶች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
30ኛው የአፍሪካ ዋንጫን ልታዘጋጅ የነበረችው ሞሮኮ በኢቦላ ስጋት ውድድሩ በአንድ ዓመት እንዲሸጋሸግላት ብትጠይቅም ካፍ አስተናጋጅነቷ ለመንጠቅ ከውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ ሞሮኮን በመተካት አፍሪካ ዋንጫውን የሚያዘጋጅ አገር በሚቀጥለው ሳምንት ይታወቃል፡፡ አዘጋጁ ወዳልታወቀው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፉ ቡድኖችን የሚለዩት የማጣርያ ግጥሚያዎች ሰሞኑን በመላው አህጉሪቱ ይቀጥላሉ፡፡  አልጄርያ እና ኬፕቨርዴ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ሁለት አገራት ናቸው፡፡ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 2 ከአልጄርያ፤ ከማሊ እና ከማላዊ ጋር ሲደለደል የማለፍ ተስፋ እንደነበረው ይገለፅ ነበር፡፡ ዋልያዎቹ ቢያንስ በምድባቸው በሁለተኛ ደረጃ በመጨረስ ወይንም ከሁሉም ምድቦች ምርጥ ሦስኛነት ያልፋል የሚል ግምትም ተሰጥቷል፡፡  ባደረጋቸው አራት የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ቢያንስ 6 ነጥብ ሊያገኝ ቢገባውም ስላልሆነለት ግን የማለፍ ዕድሉ ጠቦበታል፡፡  በሶስቱ ጨዋታዎች  ሲሸነፍ አንዱን ከሜዳው ውጭ በማላዊ 3ለ2 እንዲሁም ሁለቱን በሜዳው በአልጄርያ እና በማሊ በተመሳሳይ 2ለ0 ውጤት በመረታቱ ነበር፡፡ በማጣርያው አራተኛ ዙር ጨዋታ ግን ከሜዳ ውጭ ማሊን 3ለ2 ሲያሸንፍ ፤ እድሉን ሙሉ ለሙሉ ከመመናመን አድኖታል፡፡ በ3 ነጥብ እና በ3 የግብ እዳ 3ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በሚቀሩት  ሁለት የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ዋልያዎቹ ከ4 ነጥብ በላይ ማግኘታቸው ተስፋቸውን ያጠናክረዋል፡፡ በተለይ ሁለቱ  ግጥሚያዎች ለማሊና ለኢትዮጵያ ወሳኝነት አላቸው፡፡ አልጄርያ ማለፏን ብታረጋግጥም በሁለቱም ቀሪ ጨዋታዎች ቡድናቸው በሙሉ አቋም በመሰለፍ ለማሸነፍ መዘጋጀቱን አሰልጣኙ ከሰሞኑ ተናግረዋል፡፡ በአፍሪካ የእግር ኳስ ደረጃ በአንደኛነት የተቀመጠችው አልጄርያ በዓለም ያለችበት 15ኛ ደረጃ በአህጉሩ ቡድን የተመዘገበ ከፍተኛ ስኬት ነው፡፡ ዘንድሮ የአልጄርያው ክለብ ኢኤስ ሴቲፍ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን  ማግኘቱን ጨምሮ ብሄራዊ ቡድኑ ከመንፈቅ በፊት በተሳተፈበት 20ኛው የዓለም ዋንጫ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ለጥሎ ማለፍ በመድረስ አስደናቂ ስኬት ማስመዝገቡ ከባድ ቡድን ያደርገዋል፡፡ ቀይ ቀበሮዎችን የሚያሰለጥኑት ፈረንሳዊው ክርስቲያን ጉርኩፍ አገሪቱን ለአፍሪካ ዋንጫ ድል ለማብቃት ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡   23 ተጨዋቾች ከሁለት ሳምንት በፊት ጠርተዋል፡፡ ተጨዋቾቹ ከአውሮፓ አገራት ስፔን፤ እንግሊዝ፤ ጣሊያን፤ ፈረንሳይ፤ ፖርቱጋል እና ቱርክ ሊጎች ከሚወዳደሩ ክለቦች የተውጣጡ ናቸው፡፡  ሲድ ሙሳ በተባለው እና በአልጀርስ ከተማ በሚገኘው ብሄራዊ የልምምድ ማእከል  ለ10 ቀናት ዝግጅት ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል በምድብ 2 ሌላ የ4ኛ ዙር ጨዋታ ማሊ እና ማላዊ ይገናኛሉ፡፡ ይህ ግጥሚያ በተለይ ለምእራብ አፍሪካዋ ማሊ ወሳኝ ይሆናል፡፡ ማላዊ ብታሸንፍ ደግሞ ውጤቱ የኢትዮጵያን ዕድል ይደግፋል፡፡ የኢትዮጵያ የመጨረሻ ተጋጣሚ የሆነችው ማላዊ ከወር በፊት  በበጀት እጥረት  ለመውጣት አመንትታ በምድቡ ያደረጋቻቸው የጨዋታ ውጤቶች እንደሚያሰርዝ መዘገቡም ለኢትዮጵያ የማለፍ እድል ፈጥሮ ነበር፡፡ ሰሞኑን ግን ኤርቴል የተባለ ኩባንያ ለማላዊ ፌደሬሽን የበጀት ድጋፍ በመስጠቱ ስጋቱን አብርዶታል፡፡ ማላዊ ከውድድሩ ብትወጣ ኖሮ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የገንዘብ ቅጣት እና የ2 አመት እግድ ሊጥልባት ይችል ነበር፡

ሰሞኑን  በቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ በተካሄደው የእስያ ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ስብሰባ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ በስብሰባ ማዕከሉ ውስጥ ማስቲካ ሲያኝኩ መታየታቸው ቻይናውያንን ክፉኛ እንዳስቆጣ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ኦባማ ቤጂንግ ከደረሱበት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ፣ በወጡ በገቡ ቁጥር ማስቲካ ሲያኝኩ እንደነበር የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ይፋ መደረጋቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ የኦባማ ድርጊት የቻይናን ታዋቂ ምሁራን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን እንዳስቆጣ ጠቁሟል፡፡ኦባማ በዚህ ታላቅ ስብሰባ ላይ ማስቲካ ማኘካቸውን ቻይናውያን በንቀት እንደተረጎሙትና ሲና ዌቦ የተባለው የአገሪቱ ታዋቂ ማህበራዊ ድረገጽም፣ ኦባማን በሚተቹ አስተያየቶች መጥለቅለቁን ዘገባው ገልጧል፡፡“ገና ከመኪናቸው ሲወርዱ ጀምሮ፣ እንደ ስራ ፈት ማስቲካ እያኘኩ ነበር” ብለዋል በቢጂንግ ሲንጉሃ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ይን ሆንግ፣ ድርጊቱን በማውገዝ በጻፉት ጽሁፍ፡፡
ማስቲካ ማኘክ በአንዳንድ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት፣ እንደ ነውር እንደሚቆጠር የጠቆመው ዘገባው፣ ሲንጋፖር ማስቲካ ወደ ግዛቷ እንዳይገባ የሚከለክል ህግ እንዳወጣችና በጃፓንም በስራ ላይ ማስቲካ ማኘክ ክልክል እንደሆነ አመልክቷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

አስገድዶ መድፈር የፍቅር መግለጫ ይሆናልን?
ወንዶች ሴቶችን ወይንም ሴቶች ወንዶችን አስገድደው ሲደፍሩ ምክንያታቸው ምንድነው?
ከላይ ለተጠቀሱት ጥያቄዎች ባለሙያዎች የሚሰጡት ምላሽ፡-
አስገድዶ መድፈር የፍቅር መግለጫ አይደለም፡፡ ሰዎች በሚፋቀሩበት ጊዜ አንዱ ለአንዱ ከማሰብ ውጪ አካልንና ስነልቡናን የሚጎዳ ነገር በፍጹም አይፈጽሙም፡፡
ወንዶች ሴቶችን ወይንም ሴቶች ወንዶችን አስገድደው የሚደፍሩበት ምክንያት ኃይልን ለማሳየት፣ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ተገዶ መደፈር እና ተመሳሳይ ጉዳት የደረሰባቸው ከሆኑም እንደ ብቀላ በመሳሰለው ምክንያት ነው፡፡
በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው በአዳማ ከተማ በአንድ ወንድ ልጅ ላይ የደረሰ ተገዶ መደፈርን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና አቶ መኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ የሰጡትን ሐሳብም እናስነብባችሁዋለን፡፡
የልጁ ምስክርነት የሚከተለው ነው፡፡
“...ሰውየው አብሮኝ ለነበረው ሰው እንዲህ አለው፡፡ ...ያንን ጥቁር ልጅ ሌሊት አስር ሰአት ላይ ስራ ስለአለኝ ለዛ ጉዳይ ስለምፈልገው ጥራልኝ... አለው፡፡ እኔም ላነጋግረው ስወጣ አስቀድሞ እጄን ነበር የያዘኝ፡፡ ጊዜው እኮ መሽቶአል ስለው ...ግድየለም... ዋጋ እንነጋገራለን...በለሊትም ሰው ከምንቀሰቅስ ከእኔ ጋር ብታድር ይሻልሀል አለኝ፡፡ እኔም ግድ የለም ዋጋ ንገረኝና እመለሳለሁ ብዬ ተከተልኩት፡፡ ከዚያ በሁዋላ እቤቱ አስገብቶ በቃ...ልብስህን አውልቅ...ተኛ...የሚል ትእዛዝ ነው የሰጠኝ፡፡ በቃ... ስለፈራሁኝ ብቻ ልብሴን አውልቄ ተኛሁ...”
በአዳማ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ቢሮአቸው የሚገኘው የስነልቡና ባለሙያው አቶ መኮንን በለጠ የልጁን ሁኔታ እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡
“...የዚህ ልጅ ታሪክ... እድሜው 18 አመት ሲሆን ተወልዶ ያደገው ባሌ ሮቤ አካባቢ ነው፡፡ የዚህ ልጅ ወላጅ አባት በበሽታ ምክንያት በመሞቱ ምክንያት እናትየው ካገባችው ሰው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ጋር መግባባት ስላቃተው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ለተወለዱ ልጆች የሚደረገው እንክብካቤ እና ቤተሰቡ ለእርሱ የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ልዩነት ስለነበረው በበጎ ፍቃድ አሳዳጊዎች ምክንያት ወደ አዳማ መጥቶአል፡፡ ይህ ልጅ ወደ አዳማ ከመጣ ገና አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ሰለባ ሆኖአል፡፡ አስገድዶ የደፈረው ሰው የልጁን ታሪክ በማጥናት እና በማባበል ...እኔ ሆቴል አለኝ... ስራ አስገባሀለሁ... በማለት ሊያግባባው ሞክሮአል፡፡ ከዚያም ባገኘው እለት አስገድዶ ሲደፍረው ልጁ የነበረውን ጉልበት ተጠቅሞ በላዩ ላይ የተቀዳደደ ልብሱን በእጁ ይዞ ... አምልጦ ...ማመን በሚያቅት ሁኔታ ነበር ወደነበረበት የሄደው...”
ወደተጎጂው ስንመለስ የሰውየውን አባባል እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡
“...እኔ እኮ ወድጄህ ነው፡፡ አፈቅርሀለሁ፡፡ ገና ሳይህ ነው ልቤ የተሸበረው... ወዘተ ሲለኝ ...እኔ እኮ ሴት አይደለሁም፡፡ ለምን ታፈቅረኛለህ... ብዬ ገፍትሬው ነው ያመለጥኩት፡፡”
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ እንደሚሉት፡-
“...አስገድዶ መድፈር ብዙውን ጊዜ የሚታወቀው ወንድ ሴት ልጅ ላይ በሚያደርሰው ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት እንደሚስተዋለው ግን ወንድ ወንድን እንዲሁም ሴት ወንድን የሚደፍሩበት አጋጣሚ አለ፡፡”
ወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ መሆኑን የሚገልጹት አቶ መኮንን ቤተሰብ ይህ ነገር ሲፈጸም ቅድሚያ የሚሰጡት ሁኔታውን ለማድበስበስ እና ለመካድ እንጂ ልጆቹ የስነልቡና ድጋፍ ወይንም ፍትህ፣ ሕክምና እንዲያገኙ አይደለም፡፡ ይህ ብዙዎች የሚያደርጉት ሙከራ ሲሆን አንዳንድ ወላጆች፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ግን በፍጥነት እርምጃ የሚወስዱ መሆኑ የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል፡፡  
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ እንደሚሉት፡-
“...ብዙ ጊዜ ሬፕ (አስገድዶ መድፈር) የሚያደርጉ ሰዎች ከተመሳሳይ ጾታም ይሁን ከተቃራኒ ጾታ ባጠቃላይም ከሰዎች ጋር ጥሩ አይነት ግንኙነት መፍጠር የማይችሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ምክንያትም ከአስተዳደግ ወይንም ከተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር     ጥሩ የሆነ መግባባትና ግንኙነት መፍጠር የሚያቅታቸው ከሆነ እንደዚህ ያለውን (አስገድዶ መድፈር) የመሳሰለውን ወንጀል እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸዋል፡፡”
ተገዶ መደፈር የደረሰበት ልጅ እንደገለጸው፡-
“...ድርጊቱን ፈጻሚው ሰው በህግ እንዲጠየቅ በሚደረግበት ጊዜ... እኔ እነዚህን ሰዎች ከየት እንደመጡ አላውቅም፡፡ እንደዚህ አይነት ድርጊትም አልፈጸምኩም፡፡ ልጁንም አልጠራሁትም ...እንዲያውም አላገኘሁትም በማለት ነበር የካደው..” ብሎአል፡፡
አቶ መኮንን እንደሚገልጹትም፡-
“...ልጁ የደረሰበት ጉዳት ከፍ ያለ ስለነበር በጊዜው ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ በሚያገኝበት በዚህ ስፍራ ሲመጣ ባለሙያዎች በህግ አንጻርም ሆነ በህክምናው እንዲሁም በስነልቡናው ተገቢውን አገልግሎት በፍጥነት እንዲያገኝ ጥረት አድርገዋል፡፡ አስገድዶ ደፋሪው ምንም እንኩዋን ለመካድ ቢሞክርም በወቅቱ ልጁ እራቁቱን ...የተቀዳደደውን ልብሱን በእጁ ይዞ መምጣቱ እና ሌሎች የተለያዩ መረጃዎች በመኖራቸው     እውነቱን ለማግኘት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡”
አቶ መኮንን የህግ ባለሙያዎችን እና የህብረተሰቡን ትብብር በሚመለከትም፡-
“...ፖሊሶች ለሙያቸው ስነምግባር ተገዢ መሆን እንዳለባቸው ቢያምኑም በጣም የሚያሳዝነው ግን ...አንዳንድ ፖሊሶች ለወንጀለኛው የማገዝ ነገር ይታይባቸው ነበር፡፡ ተጎጂው ባለበት ሌላም ታዛቢ በሚገኝበት ካለምንም ፍርሀት ...እኔ ዋስ ሆኜ አስወጣዋለሁ... ምንም ችግር የለም ሲሉ የተስተዋሉ ነበሩ፡፡ አስገድዶ ደፋሪው በዚህ ድርጊቱ ቀደም ሲልም የሚታማ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሕግ ሳይቀርብ የቆየ መሆኑን እያወቁ እንደዚህ ያለ ንግግር በተናገሩ ላይ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ቢያዝኑም በሌላ በኩል ደግሞ  ለሙያቸው ተገዢ የሆኑ ጠንካራ የፖሊስ አባላት አቃቤ ሕጎች እና ዳኞች በመኖራቸው ጉዳዩን በጥንካሬ ይዘው ከዳር በማድረሳቸው ጥፋተኛው በስምንት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አስችለውታል፡፡ ምንም እንኩዋን ጉዳት የሚያደርሱ ባይታጡም ለትክክለኛው ስራቸው የቆሙትን በዚሁ አጋጣሚ ማመስገን እወዳለሁ...” ብለዋል፡፡
ሌላው አነጋጋሪው ነገር ሽምግልና ነው፡፡
ተገዶ የተደፈረው ልጅ እንደገለጸው “...የእኔ ወገኖች በሽምግልና ሲጠየቁ አይሆንም... አንቀበልም በማለት አሻፈረኝ ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ ጥፋት ተደግሞ በሌላ ሰው ሊደርስ እንደማይገባ ማስተማሪያ እና ደፋሪው ሰው በህግ መጠየቁ ለተደፋሪውም የሞራል ካሳ ስለሆነ... የሚል ነበር፡፡ ስለዚህም ገንዘብ እንክፈል... ሌላም ካሳ እንስጥ ሲባል... መልሳቸው አንቀበልም የሚል ስለነበር ወደህግ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ሆኖአል፡፡” አቶ መኮንን በዚህ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“...ሰው ለሰው መድሀኒቱ ነው፡፡ መድሀኒት የሚሆነው ግን ተገቢውንና በጎውን ነገር ሲያደርግ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ካላደረገ ግን ሰው ለሰው መድሀኒት መሆኑ ቀርቶ መርዝ ይሆናል፡፡ ሽምግልና በሰው ልጆች ዘንድ የታወቀ በጎ ባህርይ ቢሆንም አንዳድ ጊዜ የሚውልበት ቦታ ግን ጎጂ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴት ልጆች ተገደው ሲደፈሩ አስገድዶ ደፋሪው በህግ እንዳይጠየቅ ገንዘብ እንክፈል... የሞራል ካሳ እንስጥ የሚባለው ነገር ምክንያቱ ከጥቅም ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለማንኛውም... ይህ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የስነልቡና፣ የሞራል፣ የአካል ደህንነታቸው የሚጠበቀው ጉዳት አድራሹ በሚከፍለው ገንዘብ ሳይሆን በህግ ተገቢውን ፍትሕ ሲያገኙ ነው፡፡     እንደ አቶ መኮንን አባባል ሰው ሶስት ድህነቶችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡  
ሰው መንፈሳዊ ድህነትን ማሸነፍ ይገባዋል፡፡ ሁሉም ሰው እንደየእምነቱ ፈሪሀ እግዚአብሄር ሊያድርበት ይገባል፡፡ ልጆች ተገደው መደፈር ሲደርስባቸው ለጥፋት አድራሹ ወገንተኛ ሆኖ መቆምና ስለልጆቹ የወደፊት ሕይወት አለማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡
ሰው ማህበራዊ ድህነትንም ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ በማንኛውም ጊዜ ሰው ለገንዘብና ለጥቅም ሳይሆን  ለእውነት ተገዢ መሆን አለበት፡፡
ሰው በሶስተኛ ደረጃ ማሸነፍ ያለበት ድህነት የአእምሮ ድህነትን ነው፡፡ ሁሉም ሰው የተቻለውን ያህል እውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሕይወት እራስዋ ትምህርት ቤት እንደመሆንዋ ማንኛውም ሰው እውቀት እንዲኖረው እራሱን ካዘጋጀ እውቀት ይኖረዋል፡፡
ስለዚህ ... እነዚህ ሶስቱ መበደር የማንችልባቸው ድህነቶች ሲሆኑ ተበድረን ልናሸንፍ የምንችለውን የኢኮኖሚ ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ፍላጎት ከአጥፊዎች ጋር በመተባበር ወይንም ወንጀልን ለመደበቅ ሙከራ ማድረግ ያስጠይቃል ...ሰው... ሽምግልናን ከአግባብ ውጪ ለመተግበር መሞከር የለበትም፡፡

Published in ላንተና ላንቺ
Page 8 of 19