በድሮ ጊዜ አንድ አንቱ የተባሉ አገረ ገዢ በየክፍለ ሀገሩ እየተዘዋወሩ ህዝቡን እየሰበሰቡ ያነጋግሩ ነበር ይባላል፡፡ አብረዋቸው አዋጅ ገላጮች ነበሩ፡፡ አዋጅ ገላጮቹ በታወጁ አዋጆች ላይ ጥያቄ ቢነሳ የሚያብራሩ የሚገልጡ ናቸው፡፡
ህዝብ ከተሰባሰበ በኋላ፣ ባለሟሉ ይነሳና
“የአገራችን ህዝብ ሆይ! አገረ ገዢው እዚህ ድረስ የመጡት የእናንተን ማናቸውም ብሶት ሊያዳምጡ ነውና ጥያቄያችሁን አቅርቡ” ይላል፡፡
አንዱ ባላገር ይነሳል፡-
“ጌታዬ የግጦሽ መሬት አንሶናል” ይላል
አገረ ገዢው ወደ ፀሐፊው ዞረው
“ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን”
ሌላ ባላገር ይነሳል፤
“ማዳበሪያ ይሰጣችኋል ተብለን እስከዛሬ አልመጣልንም!”
አገረ ገዢው - “ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን”
ሌላ ባላገር ይነሳል - “የዘር  እህል ይታደላል ተብለን ዛሬም አልተሰጠንም”
አገረ - ገዢው - “ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን”
ሌላ ባላገር በንዴት
“ጌታዬ! ባለፈውም እንዲሁ እናስብበታለን ሲሉ ነበር፡፡ መቼ ነው በተግባር የሚፈፀምልን? ሁሌ እናስብበታለን ነው እንዴ?”
አገረ - ገዢው - “ይሄም ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን!”
ይሄ በጣም ያናደደው አንድ የጎበዝ - አለቃ አገሬውን በመወከል ይናገራል፡፡
“ጌታዬ ሆይ! በእኛ ላይ የደረሰውን በደል የሚያህል የትም አገር አይገኝም! ፍትህ ሲጠፋ አቤት የምንልበት ቦታ የለም! ጤና ሲጠፋ የምንታከምበት ቦታ የለም! ትምርት ሲጠፋ የምን ማርበት ቦታ የለም፡፡ መንገዱ ሲጠፋ አሳብረን የምንሄድበት አቋራጭ እንኳን የለም፡፡ እህል ሲጠፋ አንጀታችንን የምንጠግንበት፣ ውሃ ጥም ስንቃጠል ጥማችንን የምንቆርጥበት ምንም መፍትሄ የለንም! አሁን እናንተ እያስተዳደርን አገር እየመራን ነው ትላላችሁ? እኛ ህዝቡን ማስነሳትኮ አላጣንበትም! እናንተም ደግ ደጉን አርጋችሁልን፣ እኛም ደግ ደጉን አስበንላችሁ ብንኖር አይሻልም?” አለ፡፡
አገሬው አጨበጨበ!
አገረ ገዥውም፤
“የአገሬ ህዝብ ሆይ!
ይሄ የጎበዝ አለቃ ጥሩ ይናገራል ግን ዕድሜ የለውም! አሉ
አገሬው አሁንም አጨበጨበ!
ያ ጎበዝ - አለቃም ከዚያን ቀን በኋላ አልታየም፡፡”
ሁል ጊዜ “እናስብበታለን” አያዋጣም፡፡ አፈፃፀም ያስፈልጋል፡፡ በዘመንኛው ቋንቋ ቢሮክራሲያዊ ማነቆ (Bureaucratic red - tape) መበጠስ አለበት እንደ ማለት ነው፡፡ ጥንት ንጉሡ የወሰኑትን አስፈፃሚዎቹ ባለሟሎች “እሺ” “እሺ” እያሉ በተግባር ግን አንዷንም ነገር አያውሉም ነበር ይባላል፡፡ ይሄ ክፉኛ ያቆሰለው በደለኛ ንጉሡ ዘንድ ይቀርብና፤
“ጃንሆይ! ሁሉም ነገር ይቅርብኝና አንድ ሃያ አጋሠሥ ይሰጠኝ” ሲል አቤት ይላል፡፡
ጃንሆይም “ለምንህ ነው?” ቢሉት፣
“የሸዋን መኳንንት ‹እሺታ› የምጭንበት”፣ አለ ይባላል፡፡ ውሳኔዎች፣ መመሪያዎች፣ አዋጆች፣ ወዘተ በሥራ ላይ ካልዋሉ፣ ካለንበት ንቅንቅ አንልም፡፡ ጌቶች ቢያስነጥሱ መሀረብ የሚያቀብሉ ዓይነት ሰዎች መቼም፣ የትም ድረስ አያራምዱንም! ጉዳያችሁን ተናገሩ፡፡ ብሶታችሁን አውጡ፡፡ ጥያቄያችሁን አቅርቡ፤ ብሎ ‹እድሜህ አጭር ነው› ከሚል ይሰውረን፡፡ ለአጥቂውም ለተጠቂውም ከሚያጨበጭብ ተሰብሳቢም ይሰውረን፡፡
ያልተመለሰ ጥያቄ ያልተከፈለ ዕዳ ነው፡፡ ነገ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ዛሬ አድበስብሰን የምናልፈው ጥያቄ የነግ የቂም ቋጠሮ ይሆንብናል፡፡ ያ ደግሞ ዕድገትን ተብትቦ ያሰናክለዋል፡፡ የበላይ ወደታች የሚመራውን የበታች እንደ “ኮምፒዩተር ጌም” ሲጫወትበት የሚውል ከሆነ፤ እንኳን ትራንስፎርሜሽን መደበኛውም ዕድገት አይገኝም፡፡ “ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ” መሆን የሚመጣው ለትልቁ ስዕል አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ትናንሽ ስዕሎች በቅጡ ካልተሳሉና ሥጋና ደም ሳይለብሱ የቀሩ እንደሆነ ነው፡፡ የበታች አካላት ማያያዣ ክር ናቸው፡፡ እነሱ ከተበጣጠሱ የበላይ አካላት የሉም፡፡ ይሄ በቢሮክራሲያዊው ዓለም ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ፓርቲዎችም ዘንድ ያው ነው፡፡ ትናንሽ ስህተቶች ለግዙፍ ስህተት አሳልፈው ይሰጡናል፡፡ ያኔ ውድቀት ቅርብ ይሆናል፡፡
ሱን ሱ የተባለ የቻይና ጦር መሪ “በጦርነት ድል ማድረግ የሚደጋገም ነገር አይደለም፡፡ ሁሉ ቅርፁን ይለውጣል፣ ውሃ ሁሌም አንድ አይነት ቅርፅ የለውም - እንደመያዣው ዕቃ ይለዋወጣል፡፡ እንደባላንጣህ አካሄድ ቅርፅህን እየለዋወጥክ ድል መቀዳጀት ረቂቅ - ሊቅ (genius) ይባላል” ይለናል፡፡ ስለ ህይወት፣ ስለማናቸውም ትግል፣ ስለ ምርጫ፣ ስለለውጥ ስናስብ ሁሌም እንደሁኔታው  አካሄድን ቀይሮ በብስለት መጓዝን አንርሳ፡፡  ረቂቅ - ሊቅ የመሆን ጥበብ ይሄ ነው፡፡ በሌሎች ድክመት ላይ ከመንተራስ በራስ መተማመን ብልህነት ነው! አንዴ የሆነው ነገር ላይ ከማላዘን ይልቅ ሁኔታዎችን በሌላ አቅጣጫ ለመለወጥ (Reversal) መሞከር አዲስ ቅያስ ለማየት ይጠቅመናል፡፡ ሳይታለም የተፈታን ጉዳይ (de facto) ደግመን ደጋግመን መወትወት ያው ውሃ ወቀጣ ነው፡፡ የተሰረቀው ተሰርቋል፡፡ የተሄደው ድረስ ተሄዷል፡፡ የባላንጣችን አቅም ታውቋል፡፡ ዘዴና መላው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ስለዚህ የታወቀን መንገድ ትቶ ያልተሄደበትን መንገድ ወይም ብዙ ያልተሄደበትን መንገድ (The Road Less Travelled) ማሰብና ማስላት ይሻላል፡፡ የሆነውማ ሆኗል - “ለሰጠውም አላሳነሰው፣ ላልሰጠውም አላቀመሰው!”  

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ጥያቄው ምላሽ ባያገኝም ሊሰነዘር ግድ ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህንን በመቆጣጠር ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎት ያለ አድልዎና ያለ እንግልት እንዲያገኙ እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት አሉ፡፡ መልካም! ታዲያ እነሱ የት ሄደው ነው ይሄ ሁሉ የገንዘብ፣ የመብትና የጊዜ መበዝበዝ የተንሰራፋው?!

         ከእለታት በአንዱ ቀን እዚሁ ዋና ከተማችን ውስጥ ወደ አንድ ቦታ ለመሄድ የተሳፈርኩበት ታክሲ በሕግ ከተወሰነለት በላይ ታሪፍ አስከፈለኝ፡፡ በታክሲው የተሳፈርነው ሁላችን ጥቂት ብናንገራግርም ሹፌሩና ረዳቱ በማን አለብኝነት ላወጡት አዲስ ታሪፍ ተገዝተን የጠየቁንን ከፈልን፡፡… ሌላ ቀን ደግሞ ሌላ ታክሲ ከተለመደው/ከተወሰነለት የመጓዣ መስመር ውጪ (ለተሳፋሪው ሳይሆን ለእሱ በሚመቸው) ሲጓዝ ቆይቶ አጉል ቦታ ላይ አወረደኝ፡፡ እናም ጊዜዬን ተቀምቼ፣ ለሌላ ወጪ ተዳርጌና በፀሐይ ተንገላትቼ ያሰብኩበት ቦታ ካሰብኩበት ዘግይቼ ደረስኩ፡፡…
ሌላ እለት ደግሞ ሌላኛው ታክሲ መንግስት “አክብረህ ተጓዝበት” ብሎ አናቱ ላይ የሰቀለለትን “ታፔላ” አንብቤ ብሳፈርም ወደ ሌላ ቦታ ነው የምሄደው ብሎ አውላላ ሜዳ ላይ አስወረደኝ፡፡ ዛሬም ተንገላትቼና ለሌላ ወጪ ተዳርጌ (ታፔላ ሰጥቶ የማይቆጣጠረውን ተቋም እያማረርኩ) በብዙ ችግር መድረስ አይበሉት ካሰብኩበት ቦታ እጅግ ዘግይቼ ደረስኩ፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የሚሆነው በእኩለ ሌሊት እንዳይመስላችሁ፡፡ መንገድ ትራንስፖርት የመደባቸው የስምሪት ቁጥጥር ሠራተኞችና የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ባሉበት በጠራራ ፀሐይ ነው፡፡
አንድ እለት ደግሞ አገልግሎት ለማግኘት የሄድኩበት የአንድ የወረዳ ጽ/ቤት ሠራተኞች “ይህ የሚመለከተው እከሌን ነው፤” “የለም እከሌን ነው፤”… እያሉ ሲያንገላቱኝ ቆይተው አለምንም ውጤት ግማሽ ቀኔን ነጥቀውኝ ተመለስኩ፡፡
አንድ እለት ደግሞ ከወዳጆቼ አንዱ እንዲህ ሲል ሰማሁት፡፡ “ይገርምሀል! ውሃ ከጠፋብን ሁለት ሳምንት አለፈን፡፡ ታዲያ አሁን በዛ ለማለት ነው እንጂ አንድ ሳምንት አንዳንዴም አስር ቀን ያህል መጥፋቱ የተለመደ ነው፡፡ ታዲያ አንድ ነገር እንዳትረሱ ውሃ አልባው የውሃ መስመርና ቆጣሪው ግቢያችን ስለቆመ ብቻ በየወሩ መክፈላችን አልቀረም፡፡ የሠፈሩ ነዋሪ የነጠቁትን ውሃ እንዲመልሱለት ወደ ድርጅቱ ብዙ ቢመላለስም ሰሚ አላገኘም፡፡ ሁሌም መልሳቸው ይሰራላችኋል ነው፡፡ እነሱ ካልሆኑ ማን እንደሚሰራው አናውቅም፡፡….”
ሌላ ቀን ደግሞ ሌላኛው ወዳጃችን በጨዋታችን መሀል ይህን አለን፡፡ “ይገርማችኋል የ… ኮርስ መምህራችን ክፍል ከገባ እነሆ ሁለት ሳምንት አለፈው፡፡ እናም ጥቂት ቀን ተመላልሰን ስላላገኘነው እኛም መሄዱን ተውነው፡፡…” እኛ አድማጮቹም ይህንን ለማስፈጸም የተመደበ አካል መኖሩን እያሰብን በመገረም ተብሰለሰልን፡፡ አንድ ቀን ደግሞ…! አንድ እለት ደግሞ…! ሌላ እለት ደግሞ…! የእንግልታችን ልክና መጠን ቢተረክ አያልቅም!
ስለምን ለማውሳት እንደፈለግሁ ለመገመት አይከብድም፡፡ ዳርዳርታዬ የነገሬን አቅጣጫ ይጠቁማልና፡፡ ስለምን ዜጋ በመሆናችን ብቻ ልናገኘው የሚገባንን መብትና አገልግሎት አጣን? ይህንን ሊያስፈጽምልን ኃላፊነት የተሰጠው አካልስ ምን እየፈጸመ ነው? ማረፊያዬ ይህንን መጠየቅ ነው፡፡ የምጠይቀውም ህግ ሰጥቶ ተፈጻሚነቱን የዘነጋውን ነው- “መንግስት”ን፡፡ መጠየቄም “አንኳኩ ይከፈትላችኋል” እና “ጠይቁ ይመለስላችኋል” የሚሉት ሁለት ብሂሎች ያላቸውን ልዩነቶች ካለመገንዘብ አይደለም፡፡ መጠየቅ መልስ ለማግኘት ብቻ አይደለም ብዬ ስለማምን እንጂ፡፡
እንደ አንዲት ሀገር ዜጋ ማግኘት የሚገባንን አገልግሎት ተነፍገን ብዙ እየተንገላታን ነው፡፡ እንግልታችንን ታላቅ የሚያደርገው ደግሞ የተነጠቅነው መብትና አገልግሎት በህግ “የተሰጠንን” እና ዜጋ በመሆናችን ብቻ ልናገኘው ሲገባን የተነጠቅነው በመሆኑ ነው፡፡ ሌላ ሌላውን ለጊዜው ትተን (ችግሩ ባይተወንም) በእለት ተእለት እንቅስቃሴያችን ውስጥ ብቻ የምንንገላታባቸውን ነገሮች እናስብ፡፡ እርግጥ ነው ይህንን አስበንና ቆጥረን አንጨርሰውም፡፡ መንገላታታችን ልክ የለውም፡፡ እኛም ለምደነው አብረነው እያዘገምን ነው፡፡ ከትንሽ እስከ ትልቁ እንዳሻው እያንገላታን!
በዚህች ሀገር ዜጎቿ ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎት በቅጡ እያገኙ መሆን አለመሆናቸውን የሚከታተልና የሚቆጣጠር፤ በዚህም ያሉትን ችግሮችና እንግልቶች ለይቶ ለማስተካከል የሚሞክር የመንግስት አካል/አስፈጻሚ የምር አለ ብሎ ማለት ኩሸት ነው፡፡ ይህንን የምለው መኖር የሚገለጠው በኗሪው ተግባር ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ያለ ተግባር የተቀመጠ አካል ከመኖር ይልቅ ላለመኖር ቅርብ ነው፡፡ እንዲህም ስለማምን እላለሁ፡፡ አስፈጻሚው ምን እየፈጸመ ነው?!
የአንድ ሀገር ህዝብ፣ ዜጋ ሆኖ ለሚኖርባት ሀገር ግብር የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ይህ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ግብር የሚከፍለው ለጽድቅ ወይንም ለልገሳ አይደለም፡፡ በከፈለው ገንዘብ ልክ የተለያዩ ነገሮችን ለመግዛት/ለማግኘት እንጂ፡፡ ሰላምና ፀጥታን፣ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም ጊዜና እንግልት ቆጣቢ አገልግሎቶችን፣ ወዘተ… ለማግኘት፡፡ በመሆኑም እነዚህን ነገሮች የማግኘት መብት ብቻ ሳይሆን ስልጣንም አለው፡፡ የስልጣኑ ምንጭ ደግሞ ይህንን የሚፈጽሙለትን እና የሚያስፈጽሙለትን አካላት ደሞዝ የሚከፍላቸው እሱ በመሆኑ ነው፡፡
ይህ የአንድ ሀገር ዜጋ፣ ዜጋ ከሆነባት ሀገር ሊያገኝ የሚገባውን አገልግሎት በተመለከተ የዘርፉ ምሁራን የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡ ይህንን ይዘን ወደዚችው ወዳልሞላላት (ነገ ይሞላላት እንደው ባናውቅም) ሀገራችን ፊታችንን ስንመልስ ግን እየሆነ ያለው የተገላቢጦሽ ይመስላል፡፡ ጽሑፌን ስጀምር የጠቃቀስኳቸውንና ሠርክ የሚገጥሙንን ነገሮች እናስታውስ፡፡ ዜጎች ብንሆንም እንደ ዜጋ ማግኘት ያለብንን አገልግሎት ተነጥቀን በብዙ እየተንገላታን ነው፡፡ ለምን?! ለዚህስ ኃላፊነቱን የሚወስደው ማን ነው?
ጥያቄው ምላሽ ባያገኝም ሊሰነዘር ግድ ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህንን በመቆጣጠር ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎት ያለ አድልዎና ያለ እንግልት እንዲያገኙ እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት አሉ፡፡ መልካም! ታዲያ እነሱ የት ሄደው ነው ይሄ ሁሉ የገንዘብ፣ የመብትና የጊዜ መበዝበዝ የተንሰራፋው?!
በአንድ የመንግስት ቢሮ ውስጥ ድንገት በመገኘት አስተውላችሁ ወይንም አንድ ለእናቱ በሆነው “የቴሌቪዥን መስኮት” ላይ ተመልክታችሁ ከሆነ በመንግስት “መዋቅር” ውስጥ በርካታ አይነት የሥራ “ርዕሶች (titles)” አሉ፡፡ በተለይ “የዚህ ጉዳይ ክትትል”፣ “የዚህ ሂደት መሪ”፣ “የዚህ ጉዳይ ቁጥጥር” ወዘተ….. የሚሉ እጅግ በርካታ “ርዕሶች”፡፡ (ርዕሶች እንጂ ባለሙያዎች አላልኩም፡፡) እንግዲህ ልብ በሉ ይሄ ሁሉ “ተቆጣጣሪና ክትትል/አስፈጻሚ” እያለ ነው በየሄድንበት ስንንገላታና ጊዜያችንን ስንነጠቅ የምንውለው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ደሞዝ የምንከፍላቸው አካላት ስራቸውን እየሰሩ ስላይደለ ነው፡፡
ለምን እንደሆነ እርግጡን ባናውቅም ህግን እና መመሪያዎችን ያለመታከት የሚያወጣውና የሚቀይረው “መንግስታችን” ለህጎቹ ተፈጻሚነት ትኩረት አልሰጠም፡፡ ይህ “አሌ” የማይሉት ሀቅ ነው፡፡ ራሱ መንግስት ዞር ዞር ብሎ የምር ቢፈትሽ የሚያረጋግጠው ሀቅ!...  የችግሩ መነሻም ይሄው ነው፡፡ መንግስት ለህጉ እንጂ ለተፈጻሚነቱ ግድ ማጣቱ፡፡ ለህግ ተፈጻሚነት ትኩረት አለመስጠትና ህግ አለማውጣት ያላቸው ልዩነት አይታየኝም፡፡ ወይንም ተፈጻሚ ያልሆነ ህግ ካልተጻፈ ህግ እኩል ነው፡፡ ይህንን ድምዳሜዬን የህግ ባለሙያዎች እንዴት እንደሚያዩት ባላውቅም እኔን እንደዛ ይሰማኛል፡፡ ለህጉ ተፈጻሚነት ትኩረት አለመስጠት ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎች መነሳትና ምላሽ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ቢያንስ እነዚህ፡፡ ህጉን ለማስፈጸም በየደረጃው የተቀመጡት ሰዎች ተፈላጊው አቅም፣ ስነምግባር፣ ቁርጠኝነትና ፍላጎት አላቸው? ኃላፊነታቸውንስ ለመወጣት የሚችሉ ናቸው? እነዚህ የግድ ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡ ይህ ኃላፊነት በርካታ ፈተናዎች ያሉበት በመሆኑ አስፈላጊው የሰው ኃይል ሊመደብበት እንጂ ማንም አጋጣሚውና እድሉ የፈቀደለት “ባለሙያ” የሚል ካባ ተደርቦለት የሚሰየምበት አይደለም፡፡
እየሆነ ያለው ግን እንደሱ ነው፡፡ በአስፈጻሚነት የተሰየሙት ሰዎች ከሚጠበቁባቸው ብቃቶች ቢያንስ ከፊሉን የሚያሟሉ አይደሉም፡፡ ይህንን እንድንል የሚያስደፍረን ደግሞ ኃላፊነታቸውን በቅጡ መወጣት አለመቻላቸው ነው፡፡ ኃላፊነታቸውን መወጣት ባለመቻላቸውም ማግኘት ያለብንን አገልግሎት አጥተን ከንጋት እስከ ንጋት እየተንገላታን ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም አስፈጻሚው አካል የሚጠበቅበትን/የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ መሆን አለመሆኑን የሚቆጣጠረው ያለ አይመስልም፡፡ የሚቆጣጠረው ስለሌለም ለህጉ ተፈጻሚነት አይደክምም፡፡ ይህም ማንም እንደፈለገው መብታችንን እንዲነጥቅ ምክንያት ሆኖአል፡፡
ወደድንም ጠላንም ለዚህ ሁሉ ችግር ደግሞ እጃችንን መቀሰር የምንችለው ሀገሪቱንና ህዝቧን ለማስተዳደር “የተረከበው” እና የስርዓቱ ባለቤት ወደ ሆነው መንግስት ነው፡፡ ምክንያቱም የነገሩ ሁሉ “ራስ” እሱ ነውና፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በርካታ መንግስታት በስርዓታቸው ስር ስለሚፈጸመው ነገር ምስጋናውን እና ውዳሴውን እንጂ ወቀሳውን መስማት አይፈልጉም፡፡ ሆኖም ግን ስላልፈለጉ ብቻ ወቀሳውም ሆነ የታሪክ ተጠያቂነቱ አይቀሩም፡፡ ወደዱም ጠሉ እነሱ በሚመሩት ስርዓት ውስጥ ለሚፈጠረው ችግር ሁሉ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ብንወድም ባንወድም እውነቱ ይሄ ነው፡፡
የአንድን ህዝብ ብሶትና ትችት መስማት የማይፈልግ መንግስት ብሶቱን የሚፈጥሩትን ቀዳዳዎች ቀድሞ ቢያንስ ማጥበብ ከቻለም መዝጋት አለበት፡፡ በዚህም የዜጎቹን ችግሮች ማዳመጥና መቅረፍ አለበት፡፡ ይህንን ባላደረገበት ሁኔታ ግን ተቹኝ ብሎ መቆጣት ሌላ ምንም ሳይሆን አምባገነንነት ነው፡፡
እንደ ዜጋ ማግኘት ያለብንን አገልግሎት አጥተን መንገላታታችን (ሌላውን ትተን) የእለት ተእለት እንቅስቃሴያችንን እንኳን ፈታኝ አድርጎታል፡፡ ይህንንም ተመልክቶ መፍትሄ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ እንግልታችን ማብቂያ ያለው አይመስልም፡፡ ያም ሆኖ ግን  መጠየቅ መልስ ለማግኘት ብቻ አይደለም ብለን ስለምናምን እንጠይቃለን፡፡ አስፈጻሚው ምን እየፈጸመ ነው?!
መልካም ሰንበት!!

ፈቃድ ለማግኘት ከ1ሚ. ብር በላይ ካፒታልና 2 ሚ. ብር ዝግ ሂሳብ ያስፈልጋል
ኤጀንሲዎች ከተጓዥ ክፍያ ሊጠይቁ አይችሉም፡፡ 8ኛ ክፍል ያላጠናቀቀና የሙያ ማረጋገጫ የሌለው መሄድ አይችልም፡፡
ባለፉት 7 ወራት 50ሺ ኢትዮጵያውያን በህገ ወጥ ጉዞ የመን ገብተዋል፡፡

ወደ አረብ አገራት የሚሄዱ ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን ችግርና እንግልት ለማስቀረት በሚል ከአንድ ዓመት በላይ ተቋርጦ የቆየውን አሰራር ለማስጀመርና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ውዝግብ አስነሳ፡፡
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ወደ ውጭ አገር ሰራተኞችን የሚልኩ ኤጀንሲዎች፣ የግለሰብ ድርጅት ከሆነ አንድ ሚሊዮን ብር የሽርክና ማህበር ከሆነ ደግሞ አምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ሊኖረው ይገባል ይላል፡፡ ኤጀንሲው ለሰራተኛው መብትና ደህንነት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል 100 ሺህ ዶላር (ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ) በዝግ ሂሳብ የማስቀመጥ ግዴታ አለበት፡፡
 ኤጀንሲዎች ለስራ ወደ ውጭ አገር የላኳቸውን ሰራተኞች ለኢትዮጵያ ኤምባሲ በ15 ቀን ውስጥ ማስመዝገብና የስራ ፈቃድ ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ለሚኒስቴሩ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ኤጀንሲዎች ለሚሰጡት አገልግሎት ምንም ዓይነት ክፍያን መጠየቅ አይችሉም፡፡ ረቂቅ አዋጁ በውጭ አገር ስራ ለመሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ዕድል የሚያጠብና ህገ ወጥነትን የሚያባብስ ነው ሉ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች ተናግረዋል፡፡ ኤጀንሲዎች በስራው ለመሰማራት የሚያስችሏቸውን መስፈርቶች በሙሉ አሟልተው ለመቅረብ በእጅጉ እንደሚቸገሩና ረቂቅ አዋጁ መሻሻልና መታረም እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ የአረብ አገራት ጉዞ በመንግስት ከታገደ ወዲህ ባሉት ሰባት ወራት 50 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የመን መግባታቸውንና ባለፈው ጥቅምት ወር ብቻ በህገወጥ መንገድ የመን የገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ስምንት ሺህ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት አመልክቷል፡፡


Published in ዜና

      በአፍሪካ፣ ወደ ግጭት ቀጣናዎች እየተሰማራ በስነ-ምግባርና በሙያ ብቃት ስምካተረፉት መካከል የኢትዮጵያ መካከል ሃይል አንዱ እንደሆነ የገለፀው ዘኢኮኖሚስት መጽሔት፤ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በሰላም አስከባሪነት ጥሩ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ዘገበ፡፡
ቀደም ሲል ለሰላም አስከባሪነት የአውሮፓ ወታደሮች ሲሰማሩ እንደነበር መጽሔቱ አስታውሶ፤ ከ20 አመታት ወዲህ ግን በርካታ የአፍሪካ አገራት የአህጉራቱን ግጭቶች ለማብረድ የሰላም አስከባሪነት ስራዎችን እየተረከቡ ነው ብሏል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ፤ እምነት የሚጣልባቸው ሰላም አስከባሪ ሃይል በማሰማራት መልካም ስም እንዳተረፉ መጽሔቱ ገልጿል፡፡
በርካታ ሺ ወታደሮችንና ቁሳቁሶችን፣ ለሰላም ተልዕኮ እንዲያሰማሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል በተደጋጋሚ የሚመረጡት ኢትዮጵያና ሩዋንዳ፤ ለሚያሰማሩት ጦር የስልጠና እና የጦር መሳሪያ ወጪያቸው በተመድ እንደሚሸፈንላቸው ዘኢኮኖሚስት ገልፆ፤ ይህም የመከላከያ ሃይላቸውን ይበልጥ ዘመናዊ ለማድረግ ያግዛቸዋል ብሏል፡፡
በዚህም በተጨማሪ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት በራሳቸው ወጪ ለጦር መሳሪያ ገዢ የሚያውሉት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
የአንጐላ መንግስት ባለፈው አመት የመከላከያ በጀቱን ከ4.5 ቢሊዮን ዶላር ወደ 6 ቢ ዶላር (ወደ 120 ቢሊዮን ብር ገደማ) እንዳሳደገ መጽሔቱ ጠቅሶ፣ የናይጀሪያ መንግስትም ለአዳዲስ የጦር አውሮፕላኖች ግዢ አንድ ቢሊዮን ዶላር መመደቡን ዘግቧል፡፡
ከፍተኛ ገንዘብ ለጦር ሃይል በመመደብ በአፍሪካ ቀዳሚነቱን የያዘችው አልጀሪያየ በአመት 10 ቢ ዶላር ታወጣለች ብሏል - ዘገባው፡፡
የዛሬ 25 አመት ገደማ ሶቪዬት ህብረት የምትመራው የሶሻሊዝም አምባገነንነት ሲፈራርስ፣ በአፍሪካም በርካታ መንግስታት ከስልጣን እንደተወገዱና አንዳንዶቹም የተቃውሞ ፓርቲዎች እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ ማሻሻያ ለማድረግ እንደተገደዱ የሚታወስ ሲሆን፣ የነፃ ገበያ እና የዲሞክራሲ ስርዓት ጅምር ማሻሻያ ላይ በማተኮር ለመከላከያ ሃይል የሚያወጡት በጀት ለ15 አመታት ሳይጨምር እንደቆየ መጽሔቱ ያመለክታል፡፡
ባለፉት አስር ዓመታት ግን፣ የሃይማኖት አክራሪነትና የሽብር አደጋ፣ በዘር የሚቧደኑ ታጣቂዎችና ቡድኖች ግጭት፣ እንዲሁም የባህር ላይ ውንብድና ከፍተኛ ስጋት የሆነባቸው የአፍሪካ መንግስታት ለመከላከያ ሃይል ከፍተኛ ገንዘብ መመደብ ጀምረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን ለመጽሔቱ በሰጡት ገለፃ፣ አንዳንድ የአፍሪካ መንግስታት ጉድ የሚያሰኙ የጦር መሳሪያዎች እየገዙ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ T-72 የተሰኙ ዘመናዊ ታንኮችን ከዩክሬን ማስገባት ጀምራለች፡፡ ደቡብ ሱዳን ደግሞ መቶ ታንኮችን፡፡
ሰፊ የባህር በር ያላቸው እንደ ካሜሩን እና ሞዛንቢክ፣ ሴኔጋልና ታንዛኒያ የመሳሰሉ አገራት የባህር ሃይላቸውን በጦር መሳሪያ እያፈረጠሙ መሆናቸውን ዘኢኮኖሚክስ ጠቅሶ፣ አንጐላ ደግሞ የጦር አውሮፕላኖችን የሚሸከም ተዋጊ መርከብ ለመግዛት የጀመረችው ድርድር አስገራሚ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ አገራት ጦር፣ በስልጠናና በመሳሪያ ይበልጥ “ፕሮፌሽናል” ለመሆን እየተሻሻሉ መጥተዋል የሚለው ዘኢኮኖሚስት፣ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገባቸው ለመከላከያ ሃይል ደህና ገንዘብ እንዲመድቡ ከማስቻሉም በተጨማሪ እንደ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ ደግሞ በሰላም አስከባሪ ሃይል ተልእኮ አማካኝነት የማይናቅ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
እንዲያም ሆኖ የጦር መሳሪያ ግዢ በሁሉም አገራት ውጤታማ ሆኗል ማለት አይደለም፡፡ ኮንጐ ብራዛቪል ፈረንሳይ ሰራሽ ሚራዥ የጦር አውሮፕላኖችን ብትሸምትም፣ በብሔራዊ በዓላት የበረራ ትርዕት ከማሳየትና የበዓል ማድመቂያ ከመሆን ያለፈ ጥቅም አላስገኙም፡፡ ደቡብ አፍሪካም ከስዊድን 26 ተዋጊ አውሮፕላኖች ከገዛች በኋላ፣ በበጀት እጥረት ግማሾቹ ከአገልግሎት ውጭ የጋራዥ ሰለባ ሆነዋል፡፡
SU 30 አውሮፕላኖችን ከራሺያ የገዛችው ኡጋንዳ ደግሞ፤ ተስማሚ ሚሳይሎችን ስላልገዛች ዘመናዊዎቹን አውሮፕላኖች በአግባቡ ልትጠቀምባቸው አልቻለችም ብሏል መጽሔቱ፡፡   

Published in ዜና

ለአመት ያህል በበርሜር ወደ 110 ዶላር ንሮ የቆየው የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ፤ ካለፈው ሐምሌ ወዲህ እየወረደ በያዝነው ሳምንት ከ75 ዶላር በታች የደረሰ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ላይ መንግስት እስካሁን ቅናሽ አላደረገም።
በአመት በአማካይ ከሰባት በመቶ በላይ እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍጆታ፣ ባለፈው አመት 3.4 ቢሊዮን ዶላር (ከ65 ቢሊዮን ብር በላይ) ወጪ እንዳስከተለ ታውቋል። ሸቀጦች ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ባለፉት አራት አመታት እድገት ባለማሳየቱ አመታዊው ገቢ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ብዙም ፈቅ ባለማለቱ፣ የነዳጅ ግዢን እንኳ ለመሸፈን የማይበቃ ሆኗል።
በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ባለፈው አመት በነበረበት ቢቀጥል ኖሮ፣ በቀጣዩ አመት ኢትዮጵያ ሩብ ቢሊዮን ዶላር (5 ቢሊዮን ብር) ተጨማሪ ገንዘብ ለነዳጅ ግዢ ለማውጣት መገደዷ አይቀርም ነበር። ይሁን እንጂ፣ ያለማቋረጥ እየወረደ የመጣው የነዳጅ አለማቀፍ ዋጋ በስድስት ወራት ውስጥ ሲሶ ያህል ስለቀነሰ፣ ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ የምታውለው የውጭ ምንዛሬ ዘንድሮ እንደማያሻቅብ ተገምቷል።
 እንዲያውም የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ80 ዶላር በታች ሆኖ ከቀጠለ፣ የአንድ ቢሊዮን ዶላር (የ20 ቢሊዮን ብር ወጪ ቅናሽ ያስገኛል፡፡) በርካታ ነዳጅ አምራች አገራትን የሚቆጣጠሩ መንግስታት በአባልነት የተካተቱበት ኦፔክ የተሰኘው ማህበር፣ ሰሞኑን በነዳጅ ዋጋ ዙሪያ የተወያየ ቢሆንም፣ ውይይታቸው በአለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ለውጥ እንደማያስከትል ትናንት ቢቢሲ ዘግቧል። እየወረደ የመጣው የነዳጅ ዋጋ፣ የበርካታዎቹን መንግስታት ገቢ እንደሸረሸረ የገለፀው ቢቢሲ፣ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ያጋጥማቸዋል ብሏል። “ዋጋ እንዲያንሰራራ የነዳጅ ምርት መቀነስ አለብን” የሚል ጥያቄ ከሁለት መንግስታት በኩል እንደቀረበ ዘገባው ጠቅሶ፣ ጥያቄው በአብዛኞቹ መንግስታት ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን አመልክቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የነዳጅ ዋጋ መውረድ የጀመረው፣ በከፊል ከአለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ጋር በተያያዘ ምክንያት ቢሆንም፣ ዋናው ምክንያት ግን የአሜሪካ ኩባንያዎች ከፍተኛ የነዳጅ ምርትን የሚያስገኝ አዲስ ዘዴ በመፍጠራቸውና ተጨማሪ ነዳጅ ማምረት በመጀመራቸው እንደሆነ ፎርብስ መፅሔት ዘግቧል።
ከአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ውጣ ውረድ ጋር፣ የኢትዮጵያ መንግስት በንግድ ሚኒስቴር በኩል በየወሩ የነዳጅ ዋጋ ተመን የሚያወጣ ሲሆን፣ ከጥቂት ጊዜያት በስተቀር አብዛኛውን ጊዜ የዋጋ ተመኑ በነበረበት እንዲቀጥል አልያም የአለም ገበያን ተከትሎ እንዲጨምር ሲወስን መቆየቱ ይታወሳል።
ባለፉት ስድስት ወራትም እንዲሁ፣ በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በፍጥነት እየወረደ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ግን የችርቻሮ ዋጋ በነበረበት ደረጃ እንዲቀጥል አልያም እንዲጨምር የተደረገ ሲሆን፣ በያዝነው ወር መጨረሻ የዋጋ ተመኑ ላይ ምን አይነት ለውጥ እንደሚደረግበት ገና አልታወቀም። በተለመደው የመንግስት አሰራር፣ የዋጋ ተመን ውሳኔው በይፋ እስከሚገለፅበት እለትና ሰዓት ድረስ በሚስጥር ተጠብቆ ነው የሚቆየው።

Published in ዜና

የመስተዳድሩ ከንቲባ ጽ/ቤት ሠማያዊ ፓርቲን በጥብቅ አስጠንቅቋል
ዘጠኝ የ9 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነገ እሁድ የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ የእውቅና ጥያቄውን የሚቀበል የመንግስት አካል ቢያጣም ስብሰባውን ከማከናወን ወደኋላ እንደማይል አስታውቋል፡፡ የከንቲባ ፅ/ቤቱ ቀደም ሲል ህዳር 7 ሊካሄድ የነበረውን የአደባባይ ስብሰባ ተከትሎ ለሰማያዊ ፓርቲ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሠጥቷል፡፡
ነገ እሁድ ህዳር 21 ቀን የአደባባይ ስብሰባ ለማካሄድ በመኢዴፓ በኩል የእውቅና መጠየቂያ ደብዳቤው ለአዲስ አበባ መስተዳድር የከንቲባ ለመስጠት በተደጋጋሚ ሞክረው አለመሣካቱን ገልፀዋል፡፡ የከንቲባ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ደብዳቤውን ሊቀበሉን ፍቃደኛ አልሆኑም ያሉት የተቃዋሚ አመራሮች “ቢሮ ውስጥ ደብዳቤውን ስናስቀምጥ ‹ወንጀል ነው› በማለት ሃላፊው ሊያስፈራሩን ሞክረዋል” ብለዋል፡፡
ደብዳቤውን ህዳር 12 ቀን በኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት የፈጣን መልዕክት (ኢ.ኤም.ኤስ) አገልግሎት ልኮናል ብለዋል አመራሮች ነገር ግን አንድም የመስተዳድሩ አካል ደብዳቤውን ለመቀበል ፍቃደኛ እንዳልሆነ ከፖስታ አገልግሎቱ እንደተገለፀላቸው የትብብሩ አመራሮች ሰሞኑን በሠማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በነገው እለት ሊያካሂድ ያቀደውን የአደባባይ ስብሰባ ትብብሩ እንደማይሠርዝ የገለፁት ሊቀመንበሩ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ደብዳቤውን በድጋሚ ወደ ከንቲባ ጽ/ቤት በአካል ይዘው እንደሚሄዱና የማይቀበሏቸው ከሆነም በሩ ላይ እንደሚለጥፉ ገልፀዋል፡፡ የአንድ ወር ጊዜ ተይዞለት በትብብሩ የተጀመረው የአደባባይ ስብሰባ ዘመቻ “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚል መርህ ከምርጫ በፊት “ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ” እና ብሔራዊ መግባባት እንዲሁም ምርጫው ነፃ ፍትሃዊ፣ አሣታፊ፣ ተአማኒ መሆን በሚችልበት ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በማሰብ የተጀመረ መሆኑን አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል በሠማያዊ ፓርቲ አስተባባሪነት ህዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም በተመሳሳይ “የትብብሩ አባል በሆነው ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚል መርህ የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ተጠርቶ የነበረ ሲሆን ስብሰባው ጥቂት ሠዎች በተገኙበት ከተጀመረ በኋላ በፖሊስ መበተኑ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎም ስብሰባውን ሲያስተባብሩ ነበር የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ፍ/ቤት ቀርበው ምርመራ እየተጣራባቸው ነው መባሉ ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት በቀን 11/03/07 በቁጥር አ.አ/ከፅ/03/304/43 በሠማያዊ ፓርቲ “የተደረገውን ህገወጥ ተግባር በማስመልከት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ” በሚል በተፃፈ ደብዳቤ ፓርቲው ምንም አይነት የአደባባይ ስብሰባ እውቅና እንዳላገኘ እያወቀ ህዳር 6 ቀን 2007 ዓ.ም የቅስቀሳ በራሪ ወረቀት በመበተንና ህገ - ወጥ የአደባባይ ስብሰባ ለማድረግ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር አላስፈላጊ ግብግብ በመፍጠርና ጩኸት በማሰማት የአካባቢውን ህብረተሰብ ፀጥታና ሠላም የማወክ ተግባር ተከናውኗል ብሏል፡፡ ድርጊቱም ፓርቲው ህግን ተከትሎ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በህገወጥ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ያለ መሆኑን እንደሚያሳይ በደብዳቤው የጠቆመው ጽ/ቤቱ፤ በቀጣይ ፓርቲው ህግን አክብሮ የማይንቀሳቀስ ከሆነ ድርጊቱ ፀረ - ህገመንግስት ስለሆነና የከተማዋን ህዝብ ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ በጥብቅ አስጠንቅቋል፡፡  “የእውቅና ስጡን ጥያቄያችንን የሚቀበለን አካል አጣን” የሚለውን የተቃዋሚዎቹን አቤቱታ በተመለከተ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉትን የስራ ኃላፊ በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ስብሰባ ላይ ናቸው በመባላችን ሊሳካልን አልቻለም፡፡

Published in ዜና

የኢቦላ በሽታን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ዘመቻ 1100 በጐ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን መመዝገባቸውንና ከእነዚህ መካከል 210 የሚሆኑት በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ በሸታው ወደሚኝባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት እንደሚሄዱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት የአፍሪካ ህብረት ባቀረበው ጥሪ መሰረት ኢትዮጵያ በጐ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎችን በሽታው ወደሚገኝባቸው አገራት ለመላክ እንቅስቃሴ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በዚህ መሰረትም በአገሪቱ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በቀረበው ጥሪ መሰረት 1100 የሚሆኑ በጐ ፈቃደኛ የጤና ባሙያዎች ማለትም ዶክተሮች፣ የህብረተሰብ ጤና መኮንኖች፣ ነርሶች፣ ፊልድ ኢፒዶሞሎጂስቶች፣ ሳይካትሪስቶች፣ ሳይኮሎጂስቶች፣ የአካባቢ ጤና፣ የጤና ትምህርት፣ የላብራቶሪና የፋርማሲ ባለሙያዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከእነዚህ ተመዝጋቢዎች መካከልም 210 የሚሆኑት ተመርጠው ወደስፍራው እንዲሄዱ ተወስኗል፡፡ እነዚህ ተጓዦች ወደ ስፍራው ከመንቀሳቀሳቸው በፊት በቂ ስልጠናና ትምህርት የተሰጣቸው ሲሆን በሽታው ወደሚገኝባቸው የምዕራብ አፍሪካ ሶስት አገራት ማለትም ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮንና ጊኒ እንደሚጓዙም ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቴክኒካል አማካሪ ዶ/ር መርሃዊ ይርዳው እና የሚኒስቴር መ/ቤቱ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አህመድ አሚኖ በጋራ በሰጡት በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት አገሪቱ ከህብረቱ የቀረበላትን ጥሪ ተቀብላ በግንባር ቀደምትነት አጋርነቷን ለማሳየት የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ ወደ ስፍራው ለመጓዝ በርካታ ቁጥር ያላቸው በጐ ፈቃደኛ ኢተዮጵያውያን ተመዝግበዋል፡፡ አገሪቱ ባለሙያዎችን ወደ ስፍራው ከመላኳም በተጨማሪ 500ሺ የአሜካን ዶላር በሽታው ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ ታደርጋለች፡፡
በጐ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎቹ በተባበሩት መንግስታት ስታንዳርድ መሰረት የሚከፈላቸው መሆኑንና የክፍያው መጠንም ወደፊት እንደሚገለፅ ተናግሯል፡፡ የበጐ ፈቃድ ተጓዦቹ በያዝነው ወር መጨረሻ ወደ ስፍራው እንደሚጓዙም ኃላፊዎቹ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

         የቴሌቪዥን አገልግሎትን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር በቅርቡ የዲጂታል ቴሌቪዥን መሳሪያዎች ግዥና የግንባታ ጨረታ እንደሚወጣ ተጠቆመ፡፡
ለዲጂታል ቴክኖሎጂው አገልግሎት አስፈላጊ የሆኑ ትራንስሚተሮችና ልዩ ልዩ መሳሪያዎች ግዥ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በኩል እንዲካሄድ፣ አጠቃላይ የፕሮጀክት አስተዳደሩንና የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንዲከታተለው ተወስኗል፡፡ በቅርቡ ጨረታውን ለማውጣት ቅድመ ዝግጅቱ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የመሳሪያዎቹ ግዥ፣ ተከላና ግንባታም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የዲጂታል ቴሌቪዥን ስርጭት አገልግሎትን ለማግኘት የዲጂታል መቀበያ መሳሪያዎች (ሴት-ቶፕ ቦክስ) ዲጂታል ኢንተግሬትድ ቴሌቭዥን (IDTV) እና አንቴና በዋንኛነት የሚያስፈልጉ ሲሆን መሳሪያዎቹ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ መንግስት መሳሪያዎቹ ከቀረጥ ነጻ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ በማመቻቸት በድጎማና በረጅም ጊዜ ክፍያ ተገልጋዩ እንዲገዛቸው ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባውም መረጃው አመልክቷል፡፡
ደረጃውን ያልጠበቀ መሳሪያ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን፤ የአናሎግ ቴሌቪዥኖች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡና በአገር ውስጥ እንዳይመረቱ ለማድረግ የሚቻልበትን ጊዜ ለመወሰን የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ እንደሆነም ታውቋል፡፡

Published in ዜና
  • ለሽያጩ ሶስት አለማቀፍ ባንኮች ተመርጠዋል


የኢትዮጵያ መንግስት ለአለም አቀፍ ገበያ ለመጀመሪያ ጊዜ የቦንድ ሽያጭ ለማቅረብ ከተመረጡ አለምአቀፍ ባንኮች ጋር በለንደን ድርድር እያካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡
የቦንድ ሽያጩን እንዲያከናውኑ ከተመረጡ ባንኮች ጋር የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ እና የብሔራዊ ባንክ የስራ ሃላፊዎች በቦንዱ መጠንና ሽያጭ ክንውን ዙሪያ በለንደን ከሰሞኑ እየመከሩ ሲሆን፤ የቀረበውን የገንዘብ መጠን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማረጋገጥ ባይቻልም ፋይናንሻል ታይምስ የተባለው ጋዜጣ 1 ቢሊዮን ዶላር ሣይሆን እንዳልቀረ ጠቁሟል፡፡
በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የአለምአቀፍ ፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ጉዳዩ በድርድር ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁሞ የቀረበውን የገንዘብ መጠንና ከሽያጩ የሚገኘውን ገቢ ለምን ተግባር ይውላል የሚለውን በቀጣይ ሚኒስትሩ ራሳቸው እንደሚያሳውቁ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ገልጿል፡፡ ለአለምአቀፍ ገበያ የቀረበው የገንዘብ መጠን በመንግስት በኩል ይፋ ባይደረግም የቦንድ ግዥና ሽያጩን በውክልና የሚፈጽሙት ተመራጭ ባንኮች ይፋ ተደርገዋል፡፡
 ቢ ኤን ፒፓ ራቢስ፣ የደች ባንክ እና ጂፒ ሞርጋን የተሰኙት ባንኮች ሽያጩን እንዲያከናውኑ የተመረጡ ሲሆን ባንኮቹ ቦንዱን ለባለሃብቶች ይሸጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቦንዶቹ በኢትዮጵያ መንግስት ስም ታትመው በተመረጡት ባንኮች አማካኝነት ለአለም ገበያ ሲቀርቡ አገሪቱ በቀጥታ በእርዳታና በብድር ከምታገኘው በተጨማሪ ሌላ የብድር ማግኛ ይሆናታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የቦንድ ሽያጩ ለ10 አመት እንደሚቆይ የጠቀሰው የፋይናንሻል ታይምስ ዘገባ፤ የወለድ መጠኑም ከ6 እስከ 7 በመቶ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡
ይህም ሌላኛው በአለምአቀፍ የቦንድ ገበያ ሽያጭ ተሣታፊ የሆነችው ኬንያ ካቀረበችው የወለድ መጠን ከፍ ያለ ነው ተብሏል፡፡ሃገሪቱ ከቦንድ ሽያጩ የምታገኘውን ገንዘብ ለታላላቅ የመንገድ፣ የባቡር እንዲሁም የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ ታውላለች ተብሎ እንደሚጠበቅ የፋይናንሻል ታይምስ ዘገባ ያመለከተ ሲሆን መንግስት በበኩሉ ለየትኛው ፕሮጀክት ይውላል የሚለውን በሂደት ይፋ አደርጋለሁ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ለአለም አቀፍ ገበያ የቦንድ ሽያጭ ስታቀርብ የመጀመሪያዋ ሲሆን ጐረቤት ኬንያ 2 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ሽያጭ በማከናወን ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዋ ነች ተብሏል፡፡ ከ30 አመት በፊት እነ ቦብ ጊልዶፍ “ገና መሆኑን ያውቃሉ?” በሚል ነጠላ ዜማ እርዳታ ያሰባሰቡላት ሃገር ለአለማቀፍ ገበያ የቦንድ ሽያጭ እስከማቅረብ ደርሳለች ሲል ፋይናንሻል ታይምስ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው አመት በዓለም አቀፍ ተቋማት ባስጠናው ጥናት ሀገሪቱ የብድር እዳን በመክፈል አቅሟ የ “ቢ” ደረጃ ማግኘቷ አሁን ቦንድ ለመሸጥ ለደረሰችበት ውሣኔ አጋዥ ሣይሆን እንዳልቀረ ተመልክቷል፡፡

Published in ዜና

ሀሰተኛ የአባላት ዝርዝር በማዘጋጀት ያቋቋመው የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበር እውቅና እንዲያገኝ አስደርጐ መሬት ወስዷል የተባለው ግለሰብ በ8 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ፣ የወሰደው መሬትም ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ችሎት ባሳለፈው የፍርድ ውሳኔ በህገ-ወጡ የመኖሪያ ህብረት ስራ ማህበሩ ስም ለቦታው የተሰጡ 4 ካርታዎችም እንዲመክኑ ተወስኗል፡፡
ግለሰቡ የወሰደው መሬት 3ሺህ 456 ካሬ ሜትር መጠን ያለው መሆኑ የተመለከተ ሲሆን በሊዝ ዋጋ ስሌት 6 ሚሊዮን ብር ያወጣል ተብሏል፡፡ ፍ/ቤቱ መሬቱ ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን በውሳኔው አስታውቋል፡፡
ዘይኑ ነስሩ በተባለው በዚህ ግለሰብ ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ፤ ግለሰቡ ራሱን የማህበሩ ሊቀመንበር በማድረግ በማይታወቁ ሰዎች ስም ለማህበር የመኖሪያ ቤት ግንባታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ መሬቱን በመውሰድ ካርታ ማግኘቱ ተመልክቷል፡፡

Published in ዜና
Page 3 of 19