የመጨረሻዋ ገንዘቤ አይደለችም  ግን ቢያንስ ሁለት አዲስ ሪከርዶች ለማስመዝገብ እቅድ አላት
ሁለት አዲስ ዲባባዎች እየመጡ ናቸው
ዲባባ አትሌቲክስ ክለብ ሊመሰረት ይችላል

ገንዘቤ ዲባባ በ2015 እኤአ ከ2 በላይ የዓለም ሪከርዶችን በቤት ውስጥ እና የትራክ አትሌቲክስ ውድድሮች ማስመዝገብ እንደምትፈልግ  ተናገረች፡፡ በዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ለማግኘት ማቀዷንም አስታውቃለች፡፡ በ2014 የአይኤኤኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ በሴቶች ምድብ ከመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች ተርታ የገባችው አትሌቷ ባለፈው ሰሞን የሽልማት ስነስርዓቱ በሞናኮ ሲካሄድ የክብር እንግዳ ነበረች፡፡ በሌላ በኩል የዲባባ ቤተሰብ የአትሌቶች መፍለቂያ እየሆነ መምጣቱን ያወሳው የአይኤኤኤፍ ድረገፅ ዘገባ፤ ከገንዘቤ በኋላ ሌሎች ሁለት ታናናሽ የዲባባ እህትማቾች ወደ ስፖርቱ እያተኮሩ መሆናቸውን ጠቅሶ በቤተሰቡ ዓለም አቀፍ ክብር ያላቸው እና ወደፊትም መግነነን የሚችሉ አትሌቶች ብዛት 7 መድረሱን አመልክቷል፡፡ ከታላቅየው እጅጋየሁ ዲባባ በኋላ ቤተሰቡ ታላቋን የረጅም ርቀት ጥሩነሽ ዲባቡ ለዓለም አትሌቲክስ ያበረከተ ሲሆን የትዳርአጋሯ የሆነው ስለሺ ስህን ሲጨመርበት በስፖርቱ የተካበተውን ልምድ ያስገነዝባል፡፡ 5 ጊዜ የዓለም፤ ሶስት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎችን የሰበሰበችው አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ወደ ማራቶን ፊቷን ካዞረች በኋላ ታናሿ ገንዘቤ ወደ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረከ ብቅ ብላለች፡፡ ሌላው የቤተሰቡ ወንድም ከቤተሰቡ ጋር ሰፊ ልምምድ በመስራት የሚታወቅ ሲሆን አሁን የማራቶን ሯጭ ሆኗል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ ከዲባባ ቤተሰብ ታናሽያዋ እህት አና ዲባባ ትባላለች ብቅ ብላለች፡፡ አና ለዓለምኮከብ አትሌቶች ምርጫ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ባለፈው ሳምንት በሞናኮ በነበረችበት ወቅት የእህቷ አስተርጓሚ እና አማካሪ ሆና አብራ ነበረች፡፡ የአይኤኤፍ ዘገባ እንደሚያስረዳው ከዲባባ ቤተሰብ ከታላቋ ጥሩነሽ በኋላ የአትሌቲክስ ስፖርት ለየት ባለ የፕሮፌሽናል ደረጃ ገንቤ የወጣችበት ሆኗል፡፡ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች፤ በማይል የጎዳና ላይ ሩጫዎች፤ በቤትውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች፤ በወጣቶች እና በአዋቂ የዓለምሻምፒዮና እና የኦሎምፒክ ውድድሮች በአጭር ጊዜ ሰፊ እና ዘመናዊ ልምድ በማካበት ለውጥ አሳይታለች፡፡
 ታናሽየዋ አና ዲባባ ደግሞ ከቤተሰቡ የአትሌቲክስ ስፖርት ልምድ ከፍተኛ ተጠቃሚ ሆና ልዩ ተዓምር በአትሌቲክሱ ዓለም ማሳየቷእንደማይቀርም ዘገባው ያትታል፡፡ አትሌት ገንዘቤዲባባ ወቅቱን የጠበቀች ዓለም አቀፍ  ደረጃ ያሟላች ፕሮፌሽናል ሯጭ መሆና የልምምድ አሰራሯ እና የዓለም ሚዲያን ትኩረት መሳቧ ማስረጃዎች ይሆናሉ፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የአትሌቲክስ ልምምዷን በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ማድረጓ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከምትሰራው ልምምድ ባሻገር ለሁለት ወራት በስፔን ለአንድ ወር ደግሞ በስዊድን መዘጋጀቷ ውጤታማ አድርጓታል፡፡ ዋና አሰልጣኟ ጃማ ኤደን ይባላል፡፡  በትውልድ ሶማሊያዊ ነው፡፡ የመካከለኛ ርቀት የዓለም ሻምፒዮን ከሆኑት ጅቡቲያዊው አይናለህ ሱሌማንና ሱዳናዊው አቡበከር ካኪ የሚሰራው ይህ አሰልጣኝ ከገንዘቤ ሌላ በስሩ ሌሎች የኢትዮጵያ አትሌቶችንም ያሰለጥናል፡፡  እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ አትሌቶች አሰልጣኝ ሆኖ እየሰራ ነው፡፡ የአይኤኤኤፍ ዘገባ እንዳሰፈረው ገንዘቤ ዲባባ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ቢያንስ ሁለት የዓለም ሪከርዶችን  ለማስመዝገብ ከዋና አሰልጣኟ  በእቅድእየሰራችነው፡፡ በተለይ ከ3 ወራት በኋላ በ2 ማይል ሩጫ የዓለም ሪከርድን ለማሻሻል አሁን ትኩረት አድርጋለች፡፡ የ27 ዓመቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በ2014 የውድድር ዘመን በ1500 ፣ 3000 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድሮች እና በ2 ማይል በ15 ቀናት ልዩነት 3 የዓለም ሪከርዶችን ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡
 በውድድር ዘመኑ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና እና በኢንተርኮንትኔንታል ካፕ የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፋለች፡፡
ለዚህም ይመስላል በሞናኮ በሰጠችው መግለጫ የውድድር ዘመኑ ምርጥ ውጤት ያገኘሁበት ብላ አድንቃዋለች፡፡ በተያያዘ ዲባባ የሚለው ስም በዓለም አትሌቲክስ ስኬቱ መቀጠሉን ከሞናኮ ያወሳው የአይኤኤኤፍ ዘጋቢ ለምን የአትሌቲክስ ትምህርት ቤት አይከፈትም  በስማችሁ አትከፍቱም ብሎ ለገንዘቤ ዲባባ ጥያቄ አቅርቦላታል፡፡
 ‹‹ ወደፊት የዲባባ አትሌቲክስ ክለብ እናቋቁም ይሆናል፡፡ ጥሩ ሃሳብ ነው›› በማለት መልሳለች፡፡

ለ7 በጎአድራጎት ድርጅቶችና ለአንድ ግለሰብ 2.3 ሚ. ብር ድጋፍ አደረጉ
በኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ በጣም ዝቅተኛ ነው

        በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቀደምት የሆኑት የግል ባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያ የተመሰረቱበትን 20ኛ ዓመት እያከበሩ ነው፡፡
ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ የሚከተለው ፖሊሲ ነፃ ኢኮኖሚ እንደሚሆን የተገነዘቡ ጥቂት ባለራዕይ ምሁራን የመሰረቷቸው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባን አክሲዮን ማኅበራት 20ኛ የምስረታ በዓላቸውን እያከበሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራውና የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፀጋዬ ከምሲ 20ኛ የምስረታ በዓሉን አስመልክተው በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በማንኛውም ነገር ጀማሪ መሆን ከባድ ፈተናና ችግሮች እንዳሉት ጠቅሰው፣ ባለፉት 20 ዓመታት ያጋጠማቸውን የተለያዩ መሰናክሎችና ችግሮች በዘዴ፣ በትጋትና በቆራጥነት አልፈው አሁንም በግል ኢኮኖሚው ውስጥ ቀዳሚ መሆናቸው በጣም ከፍተኛ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ፀጋዬ የኩባንያቸውን ስኬት ሲገልፁ፡፡ በ12 ሰራተኞች ጀምረው ዛሬ 380 መድረሳቸውን ከአንድ ቅርንጫፍ ተነስተው አሁን 34 ቅርንጫፎች፣ 3 አገናኝ ቢሮዎችና ከ300 በላይ የሽያጭ ወኪሎች እንዳሉት በቅርቡ ያስመጧቸውን 2 ዘመናዊና ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ክሬኖች ጨምሮ 4 የተጎዱ መኪኖች ማንሻ ክሬኖች እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የ19 ሚሊዮን ብር መግዛታቸውንና የኩባንያው የተከፈተ ካፒታል 120 ሚሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ባንካቸው ጠንካራ የህዝብ መሰረት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንኑ የህዝብ አመኔታ መሰረት ይበልጥ ለማጠናከር የተለያዩ ዘዴዎችን ቀይሰው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የአንድ ባንክ ጥንካሬ የሚለካው በሁለት ነገሮች ጠንካራ ሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ነው፤ ያሉት አቶ ፀሐይ ዘንድሮ ማሻሽ ከተባለ የእንግሊዝ የኤቲ ኤም ኩባንያ ጋር የ3.5 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት አድርገው፣ ባደጉት አገሮች በቀዳሚነታቸው የሚታወቁ ባንኮች በሚጠቀሙበት ዩኒቨርሳል ባንክ ፊዩዥን በተባለ እጅግ ዘመናዊ ኮር ባንኪንግ ሲስተም አብዛኞቹን ቅርንጫፎቻቸውን ማገናኘታቸውንና አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ባንኩ ከ20 ዓመት በፊት በ486 ባለራስ መስራቾች፣ በ24.2 የተከፈለ ካፒታል መቋቋሙን ጠቅሰው ዛሬ የተከፈለ ካፒታል 1.4 ቢሊዮን ብር የባለ አክሲዮኖች ቁጥር ከ3, 300 በላይ መድረሱን፣ ተቀማጭ ካፒታል 17 ቢሊዮን ብር በላይ ከ10 ቢሊዮን በላይ ለተለያዩ ክፍለ ኢኮኖሚዎች ብድር መስጠቱን ጠቅላላ ሀብቱ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ማስገኘቱን (ዘንድሮ ብቻ ከ830 ሚሊዮን በላይ) ማትረፉን፣ በአንድ ቅርንጫፍ ጀምሮ 157 ቅርንጫፍ መድረሱን፣ በጥቂት ሰራተኞ ጀምሮ አሁን ከ5 ሺህ በላይ እንዳሉትና የ3.4 ቢሊዮን ቦንድ በመግዛት ከግል ባንኮች ቀዳሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በ20 ዓመት ውስጥ ምን ያህል አዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎት አመጣችሁ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ፀጋዬ በፊት ከነበረው ምንም የተለየ አዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዳላቀረቡ ጠቅሰው፣ አዲስ አገልግሎት ለማቅረብ ብዙ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ብዙ ካፒታል፣ በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል ፓኬጆቹን የሚያስተዳድር ሕግ፣ … ብዙ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ የኢንሹራንስ ኢኮኖሚው አዲስ አገልግሎቶችን ለመሸከም አቅም አላዳበረም፡፡ እነዚህ ነገሮች ባልተሟሉበት አዲስ አገልግሎት መጀመር በጣም ከባድ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ቁጥር በጣም ትንሽ ነው፡፡ ይህን ቁጥር ለማሳደግ ምን ሰራችሁ? የተባሉት አቶ ፀጋዬ ጥያቄው በጣም ትክክለኛ መሆኑን አምነው፣ የሕይወት ኢንሹራንስ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሰጠው አጠቃላይ ኢንሹራንሶች ከ5-7 በመቶ መሆኑንና ይህ አሃዝ ከማንኛውም አገር ጋር ሲነፃፀር በጣም አነስተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ከበርካታ ዓመታት በፊት ጀምሮ ተንሰራፍቶ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው በኩባንያ የህይወት ኢንሹራንስ 40 በመቶ፣ በደቡብ አፍሪካ ከ50 በላይ በርካታ ያደጉ አገሮች ከ70 በመቶ በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዋናው ችግር የኢንሹራንሶች ኩባንያዎች ለሕይወት ኢንሹራንስ ትኩረት ያለመስጠት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ በየዓመቱ ሰራተኞቻችን በዚህ ዘርፍ ይሰለጥናሉ፡፡ ነገር ግን ለመሸጥ ወደ ህዝቡ ሲሄዱ የሚያበረታታ ነገር አያዩም፡፡
የሽያጭ ሰራተኞች ገቢ ደግሞ በሸጡት መጠን ስለሆነ ተስፋ ቆርጠው ይተዋሉ፤ እኛም አናበረታታም ብለዋል፡፡ እያደገ ለወደፊት ግን የተለየ ሁኔታ እያየን ነው ያሉት አቶ ፀጋዬ የሰው ገቢ የተማረ ሰው ቁጥር እየጨመረ ሲሄድና “እግዜር ያውቃል” የሚል ሰው ቁጥር እየቀነሰ ሲሄድ የአገራችንን የሕይወት ኢንሹራንስ ሁኔታ ይቀይራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን በማለት አስረድተዋል፡፡
 እህትማማቾቹ ኩባንያዎች፣ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመውጣት ረገድ የሚያኮራ ስም እንዳላቸው ጠቅሰው በ10ኛው ዓመት በዓላቸው እንዳደረጉት ሁሉ በ20ኛው በዓላቸውም ለ7 በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ለአንድ ታዋቂና አቅመ ደካማ ግለሰብ የ2.3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ መሰረት 600 ሺህ ብር በማግኘት አንበሳውን ድርሻ ያነሳው፣ መቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ሲሆን፣ 500 ሺህ ብር በመቀበል ቀጣይ የሆነው ሃምሊን የፌስቱላ ሆስፒታል ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል እያንዳንዳቸው 300 ሺህ ድጋፍ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ድርጅትና አነስሞስ ነስብ ፋውንዴሽንም ናቸው፡፡
150 ሺህ ብር ድጋፍ የተደረገላቸው ደግሞ አበበች ጎበና የህፃናት ክብካቤና ልማት ማኅበር፣ ጆይ እና ነህምያ የኦቲዝም (የአዕምሮ ዘገምተኞች) ማዕከል ሲሆኑ ከታዋቂ ግለሰቦች ደግሞ ለታዋቂው አትሌት ለሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ 150 ሺህ ብር ተለግሰዋል፡፡   

በኢትዮጵያ የካርድ ክፍያን አስቀድሞ የጀመረውን ዳሽን ባንክ፣ ዛሬ ደግሞ ከአሜሪካው ኤክስፕረስ ጋር ባደረገው ስምምነት የኤክስፕረስ ካርድ የያዘ ሰው በኢትዮጵያ አገልግሎት ማግኘት ጀመረ፡፡ የምንሰጠው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ጥሬ ገንዘብ  ሳይዝ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሰው ዓለም አቀፍ ካርድ ከያዘ የእኛን ኤቲ ኤም በመጠቀም በውጭ ካለው ሂሳቡ ገንዘብ ማውጣት ይችላል ያሉት የዳሽን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኔ ወ/ሥላሴ በኢትዮጵያ ጥሬ ገንዘብ የማይጠቀም ህብረተሰብ ለመፍጠር የተነሳንበት ዕቅድ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ስለሆነ በአጭር ጊዜ እውን እንደምናደርግ ተገንዝበናል ብለዋል፡፡ የአሜሪካን ኤክስፕረስ ሜርቻንት ካርድ የያዘ ሰው ወይም ቱሪስት በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሳምንቱን ሙሉ 24 ሰዓት በሱፐር ማርኬቶች፣ ካፌና ሬስቶራንቶች ሆቴሎች… የፈለገውን ዕቃና አገልግሎት መግዛትም ከመቻሉም በላይ ከዳሽን ኤቲ ኤም ገንዘብ ማውጣት (መመንዘር) ይችላል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ ያ ሰው ጥሬ ገንዘብ ይዞ ባለመምጣቱ የፈለገውን ነገር ከመግዛት የሚያግደው ነገር የለም፤ ጥሬ ገንዘብ ይዞ ሲዘዋወር ከሚደርስበት የደህንነት ስጋት ነፃ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በካርድ መገበያየት ጥቅሙ ለገዥ ብቻ ሳይሆን ለሻጭ ጭምር እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ገዢው ገንዘብ ያልቅብኛል የሚል ስጋት ስለሌለበት፣ ያለገደብ የሚፈለገውን ዕቃ ወይም አገልግሎት ይገዛል ነጋዴውም ብዙ ዕቃ ወይም አገልግሎት ይሸጣል በማለት ገለፀዋል፡፡
የአሜሪካ ኤክስፕረስ በክፍያ ኩባንያነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በደህንነት፣ በአገልግሎትና በግለሰብ እውቅና እጅግ የተጠና ኃይለኛ ብራንድ ነው ያሉት ም/ፕሬዚዳንትና ጄነራል ማናጀር፣ በቱርክ የካርድ አገልግሎት ሽርክና በመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ የአሜሪካ ኤክስፕረስ ተወካይ ሚ/ር አንድሪው ስትዋሪት አሜሪካን ኤክስፕረስ ከተቋቋመ 160 ዓመታት ማስቆጠሩንና በመላው ዓለም 100 ቢሊዮን ኤክስፕረስ ካርድ ተጠቃሚ እንዳላቸው በኢትዮጵያም ከዳሽን ባንክ ጋር ተባብረው በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡  

       ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የራያ ቢራ ምርት ለመጀመር የሚያስችል ሙከራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገለፀ፡፡600 ሚሊዮን ብር ከባለ አክስዮኖች በማሰባሰብና 910 ሚሊዮን ብር የባንክ ብድር በማስፈቀድ የተቋቋመው የራያ ቢራ አክስዮን ማህበር የፋብሪካ ተከላ ስራ፣ የመጥመቂያ ማሽኖች፣ ጋኖችና የጠርሙስና የድራፍት ቢራ የማሸግያ ማሽኖች ተከላ እንዲሁም ለምርት ግብአት የሚውሉ ኬሚካሎችና የተለያዩ ማሽኖችን በማስመጣት ፋብሪካው ለምርት ዝግጁ እንዲሆን መደረጉም ተገልጿል፡፡አክስዮን ማህበሩ ባለፈው እሮብ በኢሊሌ ሆቴል አዘጋጅቶት በነበረው የባለአክስዮኖች የሼር ሰርተፍኬት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት ላይ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ አታክልት ኪሮስ እንደተናገሩት ፋብሪካው ምርቶቹን ለማምረት የሚያስችሉትን ግብአቶች በሙሉ በማሟላት ዝግጁ መደረጉንና በቅርቡም የሙከራ ምርት ማምረት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የፋብሪካ ግንባታውንና የማሽኖች ተከላ ስራውን በማጠናቀቅ ምርት ለማስጀመር የሚያስችል የደረቀና እርጥብ ሙከራ ለማድረግ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡የራያ ቢራ አክሲዮን ማህበር 2441 አባላት ያሉት ሲሆን ሰሞኑን ለባለአክሲዮኖቹ የአክሲዮን ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በትግራይ ክልል ሽራሮ ከተማና በአማራ ክልል አብርሃ ጅራ ከተማ አዳዲስ የምርት መቀበያ ቅርንጫፎችን መክፈቱን አስታወቀ፡፡
ሰሞኑን ተመርቆ  አገልግሎት መስጠት የጀመረው በትግራይ ክልል ሽራሮ የሚገኘው ቅርንጫፍ በፀለምቲ፣ አስገደ ፅምብላ፣ ታህታይ አድያቦ፣ ላዕላይ አድያቦ፣ መደባይ ዛና፣ ነአደር አዴት፣ መረብለኧ፣ ወኔለኧ፣ ቆላ ተምቤን፣ ጣንቋ አበርገሌ፣ ሰሀርቲ ሳምረ እና ወልቃይት አካባቢ የሚመረቱ ምርቶችን ለግብይት የሚያመቻች ነው ተብሏል፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው ያሉ ሌሎች ወረዳዎችም ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በአማራ ክልል የሚከፈተው የአብርሃ ጅራ ቅርንጫፍ በምዕራባዊ አርማጭሆ በሚገኙት በአብርሃ ጅራ፣ አብደራፊ ኮርሁመር፣ ጐብላ፣ ግራር ውሃ፣ መሃሪሽ እና ዘመነ መሪኬ እንዲሁም በፀገዲ በሚገኙ አካባቢዎች የሚመረቱ ምርቶች የሚቀርቡበት ይሆናል ተብሏል፡፡
በምርት ገበያው አሠራር እነዚሁ ቅርንጫፎች እንደሌሎቹ ቅርንጫፎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት ናሙና በመውሰድ፣ ክብደትና ጥራት የሚለኩበት እንዲሁም አስተማማኝ የመጋዘን አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናሉ፤ ለአርሶ አደሮቹም ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለአገሪቱ ምርት ግብይት መሻሻል የጐላ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሏል፡፡ ምርት ገበያው በአሁን ወቅት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የምርት ማስረከቢያ ማዕከላቱን ከ17 ወደ 19 ከፍ ማድረጉም ተጠቁሟል፡፡

Saturday, 29 November 2014 11:29

የምሬት ድምጾች

ሀና ላላንጎ የአስራ ስድስት አመት ታዳጊ ናት ፡፡ አየር ጤና አካባቢ  ከትምህርት ቤት ወደ ቤቷ ለመሄድ በተሳፈረችበት ሚኒባስ ታክሲ ተገዳ ከተወሰደች በኋላ በደረሰባት የቡድን የመደፈር ጥቃት ምክንያት ህይወቷ አልፏል፣ ጉዳዩ በህግ ተይዟል፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት  ሰላም ለሴቶች ከጓዳ እስከ አደባባይ  በሚል መርህ ዘንድሮ ስለሚከበረው ዘመቻ በፆታዊ ጥቃት ዝግጅት እና በሃና ጉዳይ ላይ በራስ ሆቴል ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በወቅቱ መድረኩ ላይ ስለሀና የተሰጡ አስተያየቶችን መርጠን ለጋዜጣው በሚመች መልኩ ኤልሳቤት ዕቁባይ አቅርባዋለች፡፡

“አውሬ ያለ ጫካ አይኖርም”
ዶክተር ምህረት ደበበ

ለሀና ቤተሰቦች መፅናናት እንዲሆን የሀና ሞት የብዙዎች ትንሳኤ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ሁላችንም ራሳችንን አንድ ጥያቄ እንድንጠይቅ እፈልጋለሁ፡፡ ሀናን ማን ገደላት ሀና በአንድ ቀን አልሞተችም፡፡ ሀናን የገደሏት ሰዎች አንድ ቀን አልተጠቀሙም፡፡ አንደኛ፤ ሀናን የገደላት የሀናን ገዳይ የፈጠረ ህብረተሰብ ነው፡፡ ድርጊቱን የፈፀሙ ሰዎች ሲወለዱ እና በጨቅላ እድሜያቸው እንዲህ አይነት ሰዎች እንዳልነበሩ እናውቃለን፡፡ የእኛ የእጅ ስራ ናቸው፡፡ ሁለተኛ፤ ሀና የዛን ቀን አባቷ እንደተናገሩት በብዙ ሰዎች አጠገብ እና የማዳን ሀይል ወይም ችሎታ በነበረበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለፈችው፡፡ ሀና ላይ ይህን ድርጊት የፈፀሙ ሰዎችን ብዙዎች የኮነኑ ሲሆን፤ እንዲያውም ፌስቡክ ላይ አውሬዎች ተብለዋል፣ ግን አውሬ ያለጫካ አይኖርም፡፡ እያንዳንዳችን ጫካ ሆነናል፡፡ ይዘዋት የገቡበት ግቢ ሰፊ ነው፡፡ የነዛ ሰዎች ጎረቤቶች ገድለዋታል፡፡ ቸልተኝነት ሊሆን ይችላል የአካል ሊሆን ይችላል ግን ድፍረት ነው፡፡   ድፍረት ማለት የአንድን ሰው ክብር ማዋረድ ማለት ነው፡፡ የማዳን ሀይል ያላቸው ፍትህ ማስፈፀም የሚገባቸውም ገድለዋታል፡፡ ያንን መቀበል አለብን፡፡  በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ሀናን ሆስፒታል ያሉ የጤና ባለሙያዎች ናቸው የገደሏት ፡፡ ደፍረዋታል፣ እኔ ሀኪም ስለሆንኩኝ አፍሬያለሁ፡፡ እኔ ግማሹን ጊዜዬን አሜሪካን ነው የምሰራው፡፡ እዛ ቢሆን ሊደረግ የሚችለውን ነገር ስለማውቅ ሀና ምንም ስለሆነች ብቻ ሳይሆን ሰው ስለሆነች፣ የማንም ልጅ ስለሆነች ሳይሆን ሰው ስለሆነች፡፡ ሀና የተገደለችው በደፈሯት ሰዎች ቤት ውስጥ አይደለም፡፡
በሆስፒታል ውስጥ ነው፣ ሰው እንዴት ሆስፒታል ውስጥ ይሞታል? መጨረሻ ላይ የምለው ሀናን የገደልኳት እኔ ነኝ፤ ነው፡፡
እዚህ ላይ ሶስት ትላልቅ ነገሮች አሉ አንዱ ፆታ ነው፡፡ ሁለተኛው ወሲብ ነው፡፡ ሶስተኛው ጥቃት ወይም ሀይል ነው፡፡ እያንዳንዳችን ስለወሲብ የምንናገረው እና ስለወሲብ የምናስበው ነገር እስኪስተካከል ድረስ እንዲህ አይነት ነገር አይቆምም፡፡  ህመሙ ያለው ሴቶች ላይ በተጫነው ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ወንድነት መስተካከል እስካልቻለ ድረስ  እንደዚህ አይነት ነገር አይቆምም፡፡ ይህ አይነቱ ትልቅ ድፍረት ከመፈፀሙ በፊት መንገድ ላይ ብዙ ትንንሽ ድፍረቶች አሉ፡፡ ትልቁ ድፍረት በቋንቋችን ውስጥ ታጭቋል፡፡ ቋንቋችን ምን ያህል ቫዮለንት እንደሆነ ፣ ምን ያህል የሰዎችን ክብር የሚያዋርድ እንደሆነ ከቤት እስከ መንገድ ማየት ይቻላል፡፡
ወንዶች ለሚያደርጉት ነገር ብዙ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ዛሬ እስቲ ገልብጠን እንየው፡፡  ግን ለምን አብዛኛው ወንድ እንደዛ አልሆነም፡፡ ወንድነት ምንድን ነው? ጀግንነት ምንድን ነው? ደካማን ማገዝ ፣መርዳት  እኔ አንድ የምለው ነገር አለ ሰዎች ካንገት በላይ ካላደጉ ካንገት በታች ነው የሚኖሩት፣ ካንገት በታች ደግሞ ምንም ማሰብ የሚችል ነገር የለንም፡፡ ስሜትን መግዛት የሚችል ነገር የለንም፡፡ እዚህ ብንቆጠር ሴቶች ይበዛሉ፣ ሴቶች እዚህ የመጡት ስላጠፉ ነው፡፡ መቆጣት እና መሰብሰብ የነበረበት ማን ነው ፡፡ ልክ እንደ ሀኪም ባለሙያነቴ አሁንም በወንድነቴ አፍራለሁ፣ አብዛኛው ፖሊስ ማን ነው?  ወንድ ነው ሴት ነው፣ አብዛኛው የጤና ባለሙያ ማን ነው? የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያ ማን ነው? ወንድ፡፡ እንደዚህ አይደለም ካልን ለምንድን ነው አክት የማናደርገው፡፡
 ይህ የሴቶች ጉዳይ ተብሎ ታይቶ ይሆናል፡፡ አይደለም፡፡ የወንዶች ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ልክ ድርጊቱን ከፈፀሙት ሰዎች እኩል ሀላፊነት መሸከም አለብኝ፡፡ የማህበረሰብ ለውጥ እስኪካሄድ ድረስ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡


“ከዚህ በላይ ምን ሽብር አለ”
ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ

በጣም አዝኛለሁ፣ ሆድ ብሶኛል፣ ደክሞኛል፡፡ የልብ ድካም ነገር ካለ፣ ድሮ በሽታ ነበር የሚመስለኝ፤ አሁን ግን የሚረዳ ማጣት ማለት ነው፡፡ የዛሬ ሁለት አመት ልክ እንደዚህ በኢትዮጲያ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት ትሰራ በነበረችው በአበራሽ ላይ በተፈፀመው ድርጊት ደንግጠን አሁን በአይኔ መጣ የሚል እንቅስቃሴ ጀምረን ልክ የዛሬውን አይነት ሂደት አልፈን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እዛው ተመለስን፡፡ ማንንም ከመውቀሳችን በፊት እያንዳንዳችን ራሳችንን እንጠይቅ እንደተባለው ራሴን ጠየቅኩ፡፡ እኛ እንግዲህ በተነፃፃሪ ተጠቃሚ ከሚባው የህብረተሰብ ክፍል ነን፡፡ እውቀት አለን፣ ብዙ ነገሮችን የማየት እድል አለን፣ከሌላ የተሻለ ገንዘብ አለን፡፡ ግን እየሰራን ያለነው ስራ ውጤት የማያመጣው በበቂ እየሰራን አይደለም ማለት ነው ወይስ አልቻልንበትም ወይስ ተንቀን ነው ብዬ አሰብኩ፡፡  ወጣቶቹን ሳይ፣ ዶክተር ምህረትን፣ ሀይሌ ገብረስላሴን ሳይ ደግሞ ደስ አለኝ፡፡  ሌላው ያሰብኩት ደግሞ እዚህ አገር ሰው ሁሉ የሚፈራው ፀረሽብር ህጉን ነው፡፡ ግን ከዚህ በላይ ምን ሽብር አለ? ለኔ ሽብር ማለት በሰላም ወጥቶ አለመግባት ማለት ነው፡፡ ህጉ ይቀየርልን ሳይሆን ወደ ፀረ ሽብር ሕጉ ይቀየርልን፡፡ እነሱ ስለሚፈሩ ነው ጸረ ሽብርተኛ ህግ ውስጥ የከተቱት፡፡ ትንሽ ቀን መንግስት ቀጥቀጥ ቢያደርግ ብዙ ነገር እንደሚጠፋ መገመት ይቻላል፡፡
ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ

“ይቺን አገር ያጠፋት ምንአገባኝ ነው”
አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ

የሃና ቤተሰቦችን እግዚአብሄር ያፅናቸው፡፡ይህ ነገር ዜና ሆኖ የወጣው ለምን እንደሆነ ሳንግባባ የቀረን አይመስለኝም፡፡ እንዲህ አይነቱ ድርጊት ብዙ የለም ብላችሁ ታስባላችሁ እጅግ ብዙ አለ፡፡ ሀና ስለሞተች ነገ በማህበረሰቡ ውስጥ ስለማይጠቋቆሙባት እና ሌሎች ከዚህ ጋር የተያያዙ ነገሮች ስለማይፈፀምባት እንጂ የሀና አይነት ሺዎች ናቸው - ሁሉንም ነገር በውስጣቸው ይዘው የተቀመጡ፡፡ ይቺን አገር ያጠፋት ምንአገባኝ ነው፡፡ጥቃት ሲፈፀም ብናይ ይበላት እንዲህ ሆኖ ነው እንዲህ አድርጋው ነው ይባላል፡፡ መንገድ ላይ የሆነ ነገር አጋጥሞኝ ጣልቃ ስገባ ምን አገባው ምን ቤት ነው የሚሉ አሉ፡፡ እነሱ ምን አገባቸው? እንዴት አያገባኝም?! የምኖርባት አገር እኮ ነች፡፡ ይቺን አገር ነው ጥሩ ሆና ማየት የምፈልገው ፡፡ ሌላው በጣም ያስደነገጠኝ በአምስት ሰዎች የተፈፀመ መሆኑ ነው፡፡ አምስት ሰዎች እንዴት አንድ አይነት አስተሳሰብ ውስጥ ገብተው ይህን ድርጊት ሊፈፀሙ ቻሉ፡፡ አንዱ እንኳን ጥያቄ አይፈጠርበትም? በዚች አገር ብዙ የሚሰቀጥጡ ታሪኮች አሉ፡፡ ነገር ግን ድርጊቶቹ የኛ ድምር ውጤት ናቸው፡፡ ይህን ከሰማሁ ጀምሮ ልጆቻችንን ለምን አመጣናቸው የሚል ስጋት ውስጥ ገብቼያለሁ፡፡ መፍትሄውን ከፖሊስ፣ ከፍትህ አካል ብቻ አንጠብቅ፡፡ እኔ እንዲያውም እድሜ ልክ ከማሰር በአደባባይ አርባ ጅራፍ መግረፍ ውጤት ሳያመጣ አይቀርም፡፡


Published in ህብረተሰብ
Saturday, 29 November 2014 11:29

መዘዘኛው የቶንሲል ህመም

ቶንሲል ህመም ለኩላሊት መድከም ለልብ ህመምና ለሞት ሊዳርግ ይችላል

የቀዘቀዘ ምግብን ወይም መጠጥን አብዝቶ መጠቀም አሊያም በሃይለኛ የፀሐይ ሙቀት በመመታት ይከሰታል ተብሎ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ የሚታሰበው የቶንሲል ህመም መነሻ ምክንያቱ ከእዚህ በእጅጉ የተለየና ተገቢውን ህክምና በወቅቱ ካላገኘም እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ የጤና ችግር ነው፡፡ ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች በፀሐይ ላይ መመገብ፣ እንደ አይስክሬም ያሉ የቀዘቀዙ ምግቦችን በተለይ ለህፃናት መስጠትና በከባድ ፀሐይ መመታት፤ ከቶንሲል ህመም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለውና በሽታው በባክቴሪያና በቫይረስ ሳቢያ የሚከሰት የጤና ችግር እንደሆነም የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር አብርሃም የሺዋስ ይናገራሉ፡፡
በጉሮሮአችን ውስጥ የሚገኙት የቶንሲል እጢዎች በጀርሞች ተጠቅተው ሲቆጡና ሲያብጡ የሚከሰተው ህመም ቶልሲላይተስ ተብሎ ይጠራል፡፡ እነዚህ ቶንሲሎቻችን እንዲቆጡና እንዲያብጡ በማድረግ ህመም እንዲሰማን የሚያደርጉት ባክሬቴሪያና ቫይረሶች ናቸው፡፡ የቶንሲል ህመም (ቶንሲላይተስ) በአብዛኛዎቻችን ዘንድ እጅግ የተለመደና በየጊዜው የሚያጋጥም የህመም አይነት ነው፡፡ አንድ ሰው በየዓመቱ በአማካይ እስከ አራት ጊዜ ያህል በቶንሲል ህመም ሊጠቃ ወይንም ቶንሲላይትስ ሊይዘው ይችላል፡፡
የቶንሲል ህመም በቫይረስና በባክቴሪያ ሳቢያ የሚከሰት ህመም ሲሆን ቫይረስ አመጣሹ ቶንሲላይት በአብዛኛው በቀላል የቤት ውስጥ ህክምናዎች ማለትም ጨው በተቀላቀለበት ሞቅ ያለ ውሃና በሎሚ ጭማቂ ደጋግሞ  የጉሮሮ ውስጠኛውን ክፍል በማፅዳት፣ በዝንጅብል የተፈላ ሻይና ትኩስ ነገሮችን ደጋግሞ በመጠጣት ሊድን የሚችልና ምንም ዓይነት መዘዝን የማያስከትል ህመም ሲሆን በባክቴሪያዎች በተለይም ደግሞ ስትሬፕቶኮክስ ፓዮጂንስ በተባለው ባክቴሪያ ሳቢያ የሚመጣው የቶንሲላት አይነት ግን ለከፍተኛ ህመምና ሥቃይ የሚዳርግ ከመሆኑን በላይ እስከሞት ሊያደርስ የሚችል መዘዝ የሚያስከትል ነው፡፡
የቶንሲል ህመም መንስኤ የሆነው ቫይረስ ወይንም በባክቴሪያ በተለያየ መንገድ ወደ ሰውነታችን ገብቶ ቶንሲሎቻችንን ከበከለ በኋላ ባሉት ሁለትኛ ሶስት ቀናት በህመምተኛው ላይ የበሽታው ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡ ምልክቶቹም ሃይለና ትኩሳት፣ ከባድ የራስ ምታት፣ መጥፎ ጠረን ያለው ትንፋሽ፣ የጉሮሮ ህመም፣ ለመዋጥ መቸገርና በአክት ግራና ቀኝ አካባቢ በእጅ ሲነካ የህመም ስሜት መኖር ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ህመምተኛው አፉን እንዲከፍት በማድረግ ጉሮሮው በሚታይበት ጊዜ ከምላሱ ኋላ በግራና ቀኝ የጉሮሮ ግድግዳዎች ላይ እብጠትና ቅላት ይታያል፡፡ እነዚህ የጉሮሮ ግራና ቀኝ ግድግዳ ላይ የሚገኙ የቶንሲል እጢዎች እብጠታቸው አንዳንዴ ከፍተኛ ይሆንና ጉሮሮን ሙሉ በሙሉ ሊዘጉ ይችላሉ፡፡ ባክቴሪያ ወለዱ ቶንሲላይት ከመደበኛው የቶንሲል ህመሞች ምልክቶች በተጨማሪ ከሚኖረው የበሽታው ምልክት መካከል በጉሮሮ ግድግዳዎች ላይ በሚኖረው እብጠት ላይ ነጫጭ አይብ መሰል ነጠብጣቦች /ችፍታዎች/ ሊታዩበት ይችላሉ፡፡ የቶንሲል ህመም በትንፋሽ አማካይነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና ህፃናትን በይበልጥ የሚያጠቃ የበሽታ ዓይነት ነው፡
የቶንሲል ህመም (ቶንጀሲላይትስ) ከፍተኛ ሥቃይ ያለው ህመም ቢሆንም ከህመሙ በላይ አስከፊው ነገር በሽታው ካልታከመ የሚያስከትለው መዘዝ እንደሆነ ዶክተር አብርሃም ይናገራሉ፡፡ ስትሬፕቶኮከስ ፓዪጂንስ በተባለው ባክቴሪያ ሳቢያ በሚመጣው የቶንሲል ህመም የተያዘ ሰው በአግባቡና በወቅቱ ህክምናውን ካላገኘ ከኩላሊት መድከም (ኩላሊት ሙሉ በሙሉ ሥራ ማቆም) እስከ ልብ ህመም ብሎም እስከሞት ሊያደርሱ የሚችሉ መዘዞችን ያስከትላል፡፡ በባክቴሪያ ወለዱ የቶንሲል ህመም የተያዘ ሰው ተገቢውን ህክምና ካላገኘ ቶንሲሎቹ ዙሪያቸውን ያብጡና መግል ይቋጥራሉ፡፡ የህመምተኛው አንገትም ይበልጥ መግል ወደተቋጠረበት አቅጣጫ ያዘማል፡፡ ይህም የማጅራት አለመታዘዝንና መንጋጋን እንደልብ መክፈት አለመቻልን ከማስከተሉም በላይ ታማሚው ህክምና ካላገኘ ባክቴሪያው በደም ውስጥ በመሰራጨት የኩላሊትና የልብን መደበኛ ስራ በማስተጓጎል ታማሚውን ለሞት ሊዳርገው እንደሚችል ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡ ባክቴሪያ አመጣሹ ቶንሲላይተስ ሰበብ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል አጣዳፊ የኩላሊት መድከም፣ የልብ ህመም፣ የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) የቆዳና የጉሮሮ ኢንፌክሽኖች፣ ጥቂቶቹ እንደሆኑም ዶክተር አብርሃም ተናግረዋል፡፡
ስትሬፕቶከክስ ፓዮዲኒስ በተባለው የባክቴሪያ አይነት ሳቢያ የሚከሰተውን እና እጅግ አደገኛ የሆኑ ችግሮችን የሚያስከትለውን የቶንሲል አይነት ቫይረስ አመጣሽ ከሆነውና በቀላሉ ከሚድነው የቶንሲል አይነት መለየቱ አስቸጋሪ ነው፤ ያሉት ዶክተሩ ሁሉም ዓይነት የቶንሲል ህመሞች በአግባቡና በወቅቱ ህክምና ማግኘት አለባቸው፤ የሚባለውም ለዚሁ ነው ብለዋል፡፡ በቶንሲል ህመም ሳቢያ የሚመጡ የህመም ስሜቶች በሽተኛው ህክምናውን ባገኘ ሁለትና ሶስት ቀናት ውስጥ ሊጠፉ እንደሚችሉና ቶንሲላይትን በቶሎ አለመታከም ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ የሚቆይበትን ጊዜ በማራዘም ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድሉንም በዛው መጠን እንዲጨምረው ተናግረዋል፡፡ በሽታው ከፍተኛ ሥቃይ ያለው ህመም ቢሆንም ከህመሙ ይልቅ በወቅቱ ህክምና ካላገኘ የሚያስከትለው መዘዝ እጅግ አስከፊ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አብርሃም፤ በአግባቡና በጊዜው ህክምናውን በማድረግ በሽታው ከሚያስከትለው የከፋ ጉዳት መዳን ይቻላል ብለዋል፡፡

Published in ዋናው ጤና
  • የዜጎችን መብት፣ ክብርና ደህንነት የሚያስከብር ህገ - ወጥ ደላሎችን የሚያስቀር ነው        
  • 8ኛ ክፍል ያልጨረሰና የሙያ ፈተና (CoC) ያላለፈ አይሄድም.                
  • ከበፊቱ የተሻለ ቢሆንም አሁንም ክፍተቶች አሉት ፤ ለሕገ -ወጥነት በር ይከፍታል..

              
       ለሥራ ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት የሄዱ ዜጎች (አብዛኞቹ ወጣት ሴቶች) ከፎቅ መወርወር፣ አካል መጉደል፣ በሽተኛ መሆን፣ ሞት፣ የሰሩበትን ደሞዝና ያፈሩትን ንብረት ሳይዙ ሙልጫቸውን መባረር፣ …. ብዙዎችን ያስቆጣ ድርጊት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
በተለይ ሳዑዲ አረቢያ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የውጭ አገር ዜጎች (በተለይ ኢትዮጵያውያን) በ6 ወር ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ካላወጡ ከአገሬ አባራርላሁ ስትል፣ እዚያ ከነበሩት በስተቀር እውነት ይሆናል ብሎ ነገሬ ያለውና ስጋት የገባው ብዙ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ቀነ ገደቡ አልቆ አትዮጵያውያን ከየነበሩበት እየተለቃቀሙ ክብራቸው ተዋርዶ፣ ሰው መሆናቸው ተክዶ በኢ-ሰብአዊነት ተንቆ ሲደበደቡ፣ ሲሞቱ፣ ሲታሰሩ፣ ሲሰቃዩ፣ … የብዙዎችን ትኩረት ስቦ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
መንግሥትም፣ የታሰሩ ዜጎችን ወደ አገር ከመለሰ በኋላ፣ የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያት ህገ ወጥ ደላሎች መሆናቸውን ደርሼበታለሁ፤ አሁን ያለው የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ ለህገ ወጥ ደላሎች በር የሚከፍት ስለሆነ በ6 ወር ውስጥ አሻሽዬ እስከማቀርብ የውጭ አገር ጉዞ ተሰርዟል በማለት አወጀ፡፡
በ6 ወር ተጠናቅቆ ይቀርባል የተባለው አዋጅ ዓመትም አልፎት አልተጠናቀቀም፡፡ ኤጀንሲዎች ቢሯቸውን ቢዘጉም፣ አሁንም ድረስ የውጭ አገር ጉዞ ክልክል ቢሆንም፣ ከውጭ አገር ተባርረው የመጡና በፊቱንም ወደ አረብ አገራት ለመሄድ አኮብኩበው የነበሩ ዜጎች፣ በህገወጥ መንገድ በድንበርም ሆነ በቦሌ ወደ አረብ አገራት እየሄዱ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ሪፖርት ባለፉት 6 ወራት ከ40 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውን በጦርነት እየታመሰች ወዳለችው የመን መሰደዳቸውን አመልክቷል፡፡
አሁን መንግስት የኢትዮጵያ የውጭ አገር የስራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ጨርሷል፡፡ ስለዚህ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማ፣ ከየክልሉና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በረቂቅ አዋጁ ላይ ለሶስት ቀን ውይይት አካሂዷል፡፡
አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ማለት ይቻላል አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በአፈጻጸም ረገድ ተግባራዊነታቸው የሚያጠራጥሩ ጥቂት አንቀፆች ቢኖሩትም የሰራተኞችን መብት፣ ደህንነትና ክብር ከማስጠበቅ አኳያ፣ ከበፊቱ አዋጅ ጋር ሲነፃፀር በጣም የተሻለና ጠበቅ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ተሳታፊዎች ያልተዋጡላቸው አንቀፆችም አሉ፡፡ ኤጀንሲዎች በውጭ አገር ቢሮ መክፈት አለባቸው፣ ወደ ውጭ ለስራ የሚልኳቸው ሰራተኞች 8ኛ ክፍል ያጠናቀቁና የሙያ ምዘና ፈተና (CoC) ወስደው ያለፉ መሆን አለባቸው፣ ኤጀንሲዎች ሰራተኛ ወደሚልኩባቸው አገሮች መግባትና መውጣት አለባቸው፣ … የሚሉት ተፈፃሚነታቸው አጠራጥሯል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በአምስት ቡድን ተከፍለው ሊቀመንበርና ጸሐፊ መርጠው በረቂቅ አዋጁ ላይ አንቀጽ በአንቀጽ ተወያይተዋል፡፡ በመጨረሻም በየአንቀጹ ላይ በስፋት ከተወያዩ በኋላ ይህ አንቀጽ ለምን ገባ? መስተካከል አለበት፣ አሻሚ ነው፣ ግልጽ አይደለም፣ እንዲህ ዓይነት ዓረፍተ ነገር ወይም ቃል ካልተጨመረበት ለህገ ወጥ አሰራር በር ይከፍታል፣ ይህ አንቀጽ ቢወጣ ይሻላል፣ … በማለት የተወያዩባቸውን ነጥቦች ለመድረኩ አቅርበዋል፡፡ አዘጋጁ ክፍልም የተሰጡትን አስተያየቶች አዳምጦ፣ ከቀረቡት ነጥቦች ከ70-80 በመቶ ለረቂቅ አዋጁ መሻሻል ገንቢ በመሆናቸውና፣ አንዳንድ ነጥቦች አዘጋጅ ኮሚቴው ያላያቸው ስለሆኑ እንደሚቀበላቸው፣ አንዳንዶቹ ማብራሪያ የሚሹ ሌሎቹ ደግሞ ጥያቄዎች መሆናቸውን ጠቅሶ ባለድርሻ አካላቱ ላደረጉት የነቃ ተሳትፎ ከልብ አመስግኗል፡፡
በውጭ አገር የስራ ስምሪት አገልግሎት ሰጪ ማህበር አመራሮች የውይይቱ ታዳሚ ብቻ ሳይሆኑ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ረቂቁን እንዴት አያችሁት? አልኳቸው፡፡ አቶ መዝገቡ አሰፋ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ስለረቂቁ ያላቸውን አስተያየት እንዲህ ገልጸዋል፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ ከበፊቱ 632/2001 ጋር ሲነፃፀር የራሱ መልካም ጎኖች አሉት ያሉት አቶ መዝገቡ፣ ኤጀንሲዎች፣ መንግስት ለመንግስት ተነጋግረው የሁለትዮሽ ስምምነት ወዳላደረጉት አገር ኤጀንሲዎች ሰራተኛ እንዳይልኩ መከልከሉ እኛም የምንፈልገው ስለሆነ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የዜጎችን  መብት፣ ደህንነትና ክብር ስለሚያስጠብቅ በጣም ጥሩ ነው ብለዋል፡፡
ሌላው የዚህ ረቂቅ አዋጅ መልካም ጎን ነው ያሉት ቀደም ባለው ጊዜ ሰራተኞች ወደ ውጭ አገራት ሲላኩ፣ ምንም ወጪ ስለማያወጡ አንዳንድ ሰራተኞች ለምን ሄጄ አይቼ አልመጣም? በማለት ይሄዱና አሰሪያቸውና አገሩ ከተስማማቸው ይቆያሉ፤ ካልተስማማቸው በወርና በሁለት ወር ጥለው ይመለሳሉ፡፡ ብዙ ወጪ አውጥተን ብንልካቸውም ሰራተኛዋ ስለተመለሰች፣ አሰሪው ምንም ስለማይከፍለን እንከስራለን፡፡ በዚህ አዋጅ ግን ሰራተኛዋ ምንም ሳትሰራ ብትመለስ እሷን ለመላክ ያወጣነውን ወጪ መጠየቅ እንድንችል በአዋጅ መደንገጉ ለእኛ በጣም ጥሩ ነው፤ ሰራተኞችም ኃላፊነት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ ቀደም ሲል ያልነበረ በተቀባይ አገር ሌበር አታሼ እንዲመደብ መደረጉ ሌላው የአዋጁ ጥሩ ጎን ነው፡፡ የዜጎችን መብት ከማስከበር አኳያ ለእኛም አቅም ይሰጠናል በማለት የአዋጁን መልካም ጎኖች ገልፀዋል፡፡
አዲሱ አዋጅ መልካም ብቻ ሳይሆን መጥፎ ጎኖችም እንዳሉት የጠቀሱት አቶ መዝገቡ፣ ቀደም ሲል በነበረው ህግ፣ በተለያዩ ምክንቶች የታገዱ ኤጀንሲዎች ወይም አባሎቻችን በአዲሱ አዋጅ እንዳይሳተፉ መከልከላቸው ከባድ ቅጣት ነው፡፡ በጥቃቅን ጥፋቶች የታገዱ ስላሉ ጥፋታቸው ነጥሮ ካልወጣ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሌላው ተግባራዊ መሆን አይችልም ያልነው፣ ፈቃድ ስናወጣ ወደ ተቀባይ አገር መግባትና መውጣት የምንችልበት ማረጋገጫ አምጡ መባሉ፣ በእኛ አረዳድ ብዙ የታሰበበት አይመስልም፡፡ በተሰጠው መግለጫ ይኼ ጉዳይ መንግሥት ለመንግሥት በሚያደርጉት ውል ይታቀፋል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ካለን ልምድ የሚሆን አይመስለንም፡፡
ሌላው አሳሳቢ ነገር፣ በተቀባይ አገር ሄደን ቢሮ እንድንከፍት የሚጠይቅ አንቀጽ አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር በቀድሞው ሕግ የለም፡፡ ይኼ ህግ የዚያኛውን አገር ህግ እንዴት ነው የሚያየው? ይኼ አዋጅ የሚሰራው አገር ውስጥ እንጂ ድንበር ተሻጋሪ አይደለም፡፡ የሌላ አገር ኤጀንሲ እዚህ ቢሮ ልክፈት ቢል የእኛስ መንግስት ይፈቅዳል ወይ? ይኼ ከዓለም አቀፍ ሕግም ጋር የሚጣጣም አይመስለንም፡፡
በአንቀጽ 36 እንደሰፈረው፣ ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የፍ/ቤትንም ስራ እኛው እንሰራለን እያለ ነው፡፡ እነሱው ጠያቂዎች፣ እነሱው ከሳሾች እነሱው ፈራጆች ሆነው የሚቀርቡበት ሁኔታ መሆን ያለበት አይመስለንም፡፡ የህግ አግባብ ያለው አካልስ እንዴት ነው ይህን ሁሉ ስልጣን የሚያጎናጽፋቸው? በማለት አስረድተዋል፡፡
አቶ መዝገቡ ህግ ስለወጣ ህገ ወጥ አሰራር ይቀራል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ እንዲያውም ይህ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ለህገ ወጥ አሰራር በር ይከፍታል ባይ ናቸው፡፡ ከትምህርት ጋር በተያዘ 8ኛ ክፍል ወይም 1ኛ ደረጃ ያላጠናቀቀ ወደ ውጭ አይሄድም የሚለው ለህገ ወጥ አሰራር በር የሚከፍት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “እኛ ከልምድ እንደምናውቀው ለስራ ወደ ውጭ አገራት የሚሄዱት፣ በአብዛኛው 1ኛ ደረጃ ያላጠናቀቁ ናቸው፡፡ አረብ አገር ሄደው ሁለት ወይም አራት ዓመት ቆይተው የዚያን አገር ባህል፣ ቋንቋ፣ ስራ፣ … ለምደው የተመለሱትን 1ኛ ደረጃ ስላላጠናቀቃችሁ አትሄዱም ቢባሉ እሺ! ይላሉ ወይ? በህጋዊ መንገድ ስለተከለከሉ በህገ ወጥ መንገድ ይሄዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በህገ ወጥ መንገድ ተባርረው ወደ መጡበት አገር የሚሄዱት አብዛኞቹ ቋንቋና የስራ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡
“ሌሎችም አሉ፡፡  ሾፌር፣ ግንበኛ፣ ቴክኒሻን፣ አናጢ፣ … አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ 1ኛ ደረጃን ሳያጠናቅቁ አቋርጠው ሙያ የቀሰሙ ናቸው፡፡ ሕጉ 1ኛ ደረጃን ያጠናቀቁና የሚሰጠውን የሙያ  ፈተና ያለፉ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ እነዚህ ሰዎች የሙያ ፈተናውን አልፈው 1ኛ ደረጃን ስላላጠናቀቁ ያገኙትን የስራ ልምድ መከልከል አለባቸው ወይ? ይሄ ፍትሃዊ አይመስለንም፡፡ እነዚህ ሰዎች የተከለከሉትን ዕድል በህገ ወጥ መንገድ ይሞክራሉ እንጂ ‹አሜን› ብለው የሚቀመጡ አይመስለንም፡፡ በዚህ ዓይነት ይህ ህግ ለህገ ወጦች በር ስለሚከፍት ሊታሰብበት ይገባል” በማለት አሳስበዋል፡፡
ማህበሩ፣ በአዋጁ ውስጥ መካተት አለባቸው ያላቸው ነጥቦችም አሉ፡፡ እነሱም የተቀባይና የላኪ ማኅበራት የሚያደርጉት ውሎች መንግሥት በሚያደርገው የሁለትዮሽ ስምምነት ውስጥ ተቀባይነት እንዲኖረው በህጉ ውስጥ እንዲካተት፣ አነስተኛ የኮሚሽን መጠን እንዲወሰን፣ እኛ ሰራተኞችን የምንልከው ለሁለት ዓመት ነው፡፡ ሁለት ዓመቱን ከጨረሱ በኋላ አሰሪው ከተመቻቸው ይቀጥላሉ፡፡ ይህ አሰራር በዜጎች ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ እንዴት ቢባል ኢንሹራንሳቸው ስላለቀ ጉዳት ቢደርስባቸው መካስ አይችሉም፤ ኮንትራታቸው ስላለቀ እኛም ሆንን መንግስት ወደ አገር እንደተመለሱ ነው የምንቆጥረው፡፡ እዚያ ሆነው ለሚደርስባቸው ጉዳት ወይም አደጋ ተጠያቁ አካል አይኖርም፡፡ ስለዚህ ኮንትራታቸውን ሲጨርሱ በፈቃዳቸው የሚቆዩ ከሆነ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ቆንሲላ ጽ/ቤት ወይም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከአሰሪያቸው ጋር ቀርበው ቪዛቸውና ኢንሹራንሳቸው እንዲታደስ በህጉ ውስጥ ይካተቱ በማለት መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ሚ/ር መ/ቤቱ ጥያቄዎቻቸውን ተቀብሎ በህግ አግባብ ካላቸው አይተው ፈትሸውና ተነጋግረውባቸው በአዋጁ እንደሚያካትት ቢገልጽላቸውም ማኅበሩ ግን እንዳሉት ያደርጋሉ የሚል እምነት የለውም፡፡ ምክንያቱም አሁን የተሻረው አዋጅ ከመጽደቁ በፊት በምክክር መድረክና በተወካዮች ምክር ቤት ውይይት በተደረገበት ወቅት፣ ለህገ ወጥ አሰራር በር የሚከፍቱ አንቀጾችን … ለይተው አቅርበው ነበር፡፡ ሚ/ር መ/ቤቱም ጥቆማቸውን ተቀብሎ እንደሚያርማቸው ቢገልጽም፣ አዋጁ ፀድቆ ሲወጣ ግን አንዳችም ማስተካከያ እንዳልተደረገበት ያስታውሳሉ፡፡ አሁንም፣ በውይይቱ ወቅት ያዩዋቸውን ድክመቶችና በአዋጁ መካተት አለባቸው በማለት ያቀረቧቸውን ነጥቦች ሚ/ር መ/ቤቱ በምስጋና ቢቀበላቸውም ይስተካከላሉ ወይም በአዋጁ ይካተታሉ የሚል ሙሉ እምነት እንደሌላቸው አልሸሸጉም፡፡
አቶ አበበ ኃይሌ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ አቶ አበበ ባለድርሻ አካላቱ ባደረጉት የነቃ ተሳትፎና ውይይት በጣም መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ አዘጋጁ ክፍል ያላያቸውንና ተወያዮቹ ቢጨመሩ፣ ቢቀነሱ፣ ቢስተካከሉ፣… በማለት ያቀረቧቸውን ነጥቦች በአድናቆት ተቀብለው ጥሩ ስለሆኑ በግብአትነት እንደሚጠቀሙባቸው አስታውቀዋል፡፡ አቶ አበበ በጥያቄ መልክ ለቀረቡት መልስ፣ ግልጽ ላልሆኑ ነጥቦች ደግሞ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በርካታ የቁጥጥርና የስራ አፈጻጸም ግምገማዎች የሚሰሩት በክልል ደረጃ ስለሆነ፣ ይህ አዋጅ የፌዴራልና የክልል ኃላፊነትን በተገቢው መንገድ ለይቶ ማስቀመጥ አለበት የተባለው ትክክል ስለሆነ ተቀብለነዋል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ ፈቃድ የሚሰጠው ሰው በውጭ አገር ስራና ሰራተኛ የማገናኘት አገልግሎት ለመስጠት ብቻ መሆን አለበት በሚለው አንቀጽ “ብቻ” የሚለው ቃል የገባው ሆን ተብሎ ነው ያሉት አቶ አበበ፣ ይህ አገልግሎት ከሌሎች ሥራዎች ጋር ተቀላቅሎ መሰራት የለበትም ኃላፊነት የሚጠይቅ የዕለት ተዕለት ሥራ ስለሆነ ትኩረትና ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ስራዎች ጋር ተደርቦ መሰራት የለበትም፡፡ ላኪና አስመጪ በሚል የንግድ ፈቃድ ላይ ሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ … ይላል፡፡
 ይህ አሰራር ተገቢነት የለውም፡፡ እኛ አሁን እያወራን ያለው ስለቢዝነስ አይደለም፡፡ ከዚያም በላይ ስለሆነ የሰው ጉዳይ ነው፡፡ እውቀትና ጊዜ የሚጠይቅ ስለሆነ ከሌላ ስራ ጋር የምናስተሳስረው አይደለም፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮም የሚያሳየው ይኼንኑ ነው፡፡ እና ሌላ ስራ አትስሩ አላልንም፡፡ ምርጫው የባለቤቱ ነው፡፡ እኛ ያልነው ስራና ሰራተኛ የማግኘት አገልግሎትን ከሌላ ቢዝነስ ጋር ደርቦ መስራት አይቻልም ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ካፒታሉ በዛ፣ ኤጀንሲዎችን ጥቂት ግለሰቦች በሞኖፖል እንዲይዙት ያደርጋል የሚለውን ስጋት እናየዋለን፡፡ ለስራ ወደ ውጭ አገር በሚሄዱ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው በደል እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረና እየባሰ ነው፡፡ ለዚህ የሚሆን ዋስትንና መብት ማስከበሪያም መጨመር ስላለበት ነው፡፡ በኋላ ከፍተኛ ችግር ሲያጋጥም ገንዘብ ከኪስህ አምጣ ብለን ከምናሯሯጥ መጀመሪያውኑ አስበንበት መግባት ስላለብን ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
አቶ አበበ ተሳታፊዎቹ ላነሷቸው ሌሎች ጥያቄዎችም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ ለህገ ወጥ አሰራር በር ይከፍታል አሁንም ክፍተቶች አሉት … በመባል የቀረቡትን ነጥቦች ያብራሩት የመድረኩ መሪና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ዘሪሁን ከበደ ናቸው፡፡
ዶ/ር ዘሪሁን አንድ ኤጀንሲ ዜጎችን ወደ ሚልክበት አገር በነፃ ገብቶ መውጣት የሚችል መሆን አለበት የተባለው ካጋጠመ ልምድ በመነሳት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ሰራተኞን ወደላከበት አገር መግባት የተከለከለ ኤጀንሲ፣ የዜጎችን መብት ደህንነትና ክብር ማስጠበቅ ስለማይችል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
 ቀደም ሲል ፈቃዱ የታገደበት ኤጀንሲ በዚህ አዋጅ  ፈቃድ አይሰጠውም የሚለው በጥቃቅን የአስተዳደር ጉዳዮች ጉድለት የታገደን ኤጀንሲ ሳይሆን አቤቱታ ቀርቦበት (ለምሳሌ ሬሳ አላመጣ ብሎ) የተዘጋ ኤጀንሲ ለዜጎች መብትና ክብር ደንታ ስለሌለው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄድ ሰው 8ኛ ክፍል ማጠናቀቅ አለበት የተባለው አንብቦ ሊረዳ የሚችልና ልናሰለጥነው የምንችል ዜጋ፣ አርሶ አደር … መሆን ስላለበት፣ ወደፊት 1ኛ ደረጃን ያላጠናቀቀ ዜጋ ይኖራል ብለን ስለማናስብና የእገሌ ልጅ 1ኛ ደረጃ ሳትጨርስ አይደለም ወይ የሄደችው? የሚለውን ህብረተሰብ ለትምህርት ያለውን ግንዛቤ ለመለወጥ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሀሳብ አለን…ስብስባዎች ሁሉ… አለ አይደል… “እንዴት ሰነበታችሁ…” በሚል ብቻ ይከፈትና ወደ ጉዳዩ ይገባ! አሀ…“ክቡር እከሌ እከሌ፣” “ክብርት እከሊት እከሌ፣” “የተከበሩ እከሌ እከሌ”…ምናምን ሲባል የስብሰባው ሲሦ እያለቀ ነዋ! ለነገሩ… (“ለምን ይዋሻል!” የሚሉት ነገር ነበረ አይደል!) ብዙ ስብሰባዎች ላይ “እንትንህን እንደ ዳናኪል እንፋሎት እንዳላቦንልህ!” አይነት “የጉልበት ግማሹ ምላስ ነው…” ነገር በዝቷላ! (እኔ የምለው…አንዳንዱ መድረክ ላይ ወጥቶ እንዴት ነው እንዲህ ‘ልክ ልክ ማጠጣት’ የሚዋጣለት!)
አንድ ወዳጃችን ሲነግረን አለቅየው ‘መጠመቁን’ ለበላዮቹ ለማስመስከር የማይሞክረው ነገር የለም፡፡ በተለይ ስብሰባዎች ላይ የሚናገረው ‘ቦተሊካ’ ነክ ንግግር ካርል ማርክስን ጢሙንና ጸጉሩን አርግፎለት ‘አይ ሮቦት’ ነገር ያስመስለው ነበር፡፡ እናላችሁ…በቅርብ ጊዜ ሚጢጢና የሰማይ ስባሪ አለቆችና አለቆች ነገሮችን ይሰበስብና…“እዚህ ክፍል ውስጥ የግንዛቤ ችግር ያለባችሁ ሰዎች እንዳላችሁ ይታወቃል፡፡ የኒኦ ሊበራሊዝም አስተሳሰብ መሥሪያ ቤታችን ውስጥ እንዲገባ መፍቀድ የለብንም…” ምናምን እያለ እሱ ራሱ ባልገባው ነገር ግራ እንዳጋባቸው ሲነግረን ነበር፡፡ ወዳጃችን በሆዳችን ግን ሁላችንም ቂ…ቂ… ብለናል…” ብሎናል፡፡
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ለነገሩ በሆዳችን ቂ…ቂ… የሚያሰኙ ነገሮች መአት ናቸው፡፡ ጮክ ብለን ቂ…ቂ…ብንል አበሳ ነው፣ ዝም እንዳንል  እንዴት አስችሎን — በሆድ እንኳን እንሳቅ እንጂ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሰውየው ንግግር እያደረገ ነው አሉ… እናላችሁ …ሦስት አራቱ አንድ ላይ በመናገር በየመሀሉ ያቋርጡታል፡፡ ብሽቅ ይላል፡፡ ተራ በተራ እንዲናገሩ ለማድረግም ምን ይላል… “ዛሬ እዚህ አዳራሽ ውስጥ ብዙ ደደቦች አሉ፡፡ በአንድ ጊዜ አንድ ደደብ ብቻ ቢናገር አይሻልም…” ይላል፡፡
ተሰብሳቢዎቹ ምን ቢሉት ጥሩ ነው  “…እኮ ቀጥላ!” አሪፍ አይደል! ዘንድሮ በየቦታው “…እኮ ቀጥላ!” መባል የሚገባንን ቤቱ ይቁጠረን፡፡
ስሙኝማ…“ክቡራንና ክቡራት፣ ደህና  ሁኑ፣ አትሁኑ የእኔ ጉዳይ አይደለም…ምን አግብቶኝ ነው እንደምን አደራችሁ የምለው? አሁን ወደ ስበሰባችን እንገባ፣” የሚል የክብር እንግዳ የመጣ ቀን… ያኔ የምር ዘመኑ እየገባን ነው ማለት ነው፡፡ እንደምን ብንውል ብናድር ማንም ግዴለውማ! አይደለም የእኛ ቤጤ የዓለም ሰዎችን ቀርቶ አባቶች እና ምዕመናን እንደምን አደራችሁ!... እንደምን ዋላችሁ!... እንደምን አመሻችሁ…” ሲለን እንኳን አንዳንዴ እንደው ግድ ሆኖባቸው ነው እንላለን፡፡
እኔ የምለው…አርቲስቶች (እና ‘ሴሌብሪቲዎች’…) ምናምን…አለ አይደል…በሬድዮ፣ በቲቪ ምናምን ሲቀርቡ… “እወዳችኋለሁ…” የሚሏት ነገር አሁን፣ አሁን ቂ…ቂ…ቂ… ታሰኘን ጀምራለች፡፡ ልክ ነዋ… ከዘመድ፣ አዝማድ ጋር ሁሉ ተጠማምዶ “ሸንኮራ ጠበል ቢጠመቅ ይሻላል ወይስ አርሴማ ገዳም ቢገባ…” እየተባለ ምክክር እየተደረገበት… እኛን “እወዳችኋለሁ…” ሲለን አሪፍ አይደለም፡፡ እኔ የምለው…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…አሁን አንድ አንድ ‘ቶክ ሾው’ ምናምን የሚባሉ ዝግጅቶች ላይ እየተለመደች የመጣች አባባል አለች፡፡ “እንዲህ ያሳመረኝ እንትን እንትን ቡቲክ ነው…” አይነት ነገር ይባላል፡፡ ደስ የሚል ዘመን ነው፡፡ ድሮ አፍ አውጥቶ “አምራለሁ…” ቢል የሰፈር ዕድር ሁሉ ባያድምበት ነው! ሀሳብ አለን…አንዳንድ ጊዜ… አለ አይደል… “ይህን የሚያምር ልብስ ያለበሰኝ…” ይባልልንማ! አሀ…እንደዛ ስናስብስ!  ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ የ‘ቲፎዞ ነገር’ አልበዛባችሁም! የምር አስቸጋሪ ነው…ጥሩ ነገር መሥራት ብቻውን በቂ ያልሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ “ስማ እንትን ኤፍ ኤም የምታውቀው ሰው የለህም!” መባባል ለመደብን፡፡ ምን ይደረግ!…‘ቲፎዞ’ ከሌለን ነገርዬው…አለ አይደል…“ከሌለህ የለህም…” አይነት ይሆናል፡፡
እናላችሁ…አሪፍ መጽሐፍ መጻፍ ብቻ፣ አሪፍ ዘፈን መዝፈን ብቻ፣ ብዙ የግጥም መድበል ማውጣት ብቻ፣ ጥሩ መተወን ብቻ ወዘተ. በቂ አይሆንም፡፡ በምላሳቸው “ወንድምና እህትን ማጋባት ይቻላል…” የሚባሉ አይነት ‘ሎቢይስቶች’ ያስፈልጋሉ፡፡
የምር ግን…አንዳንድ ሥራዎች ቆይተርው እናንተ ዘንድ ይደርሱና… አለ አይደል… “ይሄን ነገር እንዴት እስከ ዛሬ ድረስ አላየሁትም...” አይነት ነገር ትላላችሁ፡፡ መልሱ አጭር ነው… ‘ኖንቼ ቲፎዞ!’
ስሙኝማ… ብዙ ሠርግ ምናምን ላይ አይታችሁልኛል…ጠጁ ምናምኑ በ‘መሬት በታች መተላለፊያዎች’ (ቂ…ቂ...ቂ….) የሚሄደው ወደሚታወቁ ሰዎች፣ ወደ ሰፈር ሰዎች፣ ወደ መሥሪያ ቤት ባልደረቦች፡ ምናምን ነው፡፡ ዘመኑ የ‘ቲፎዞ’ ነዋ!
ደግሞላችሁ…አንዳንድ ቦታ የደረጃም ሆነ የደሞዝ እድገት የሚገኘውም በ‘ቲፎዞ’ ነው ይባላል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ለ‘ቲፎዞነት’ የሚያመቹ መመዘኛዎች በዝተዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ‘የአገር ልጅነት’ ዋናው ነው፡፡ እኔ እኮ አንዳንዶቹማ ከሰፊው ‘የአገር ልጅነት’ ወደ ሰፈርነት ሲወርዱ ስታዩ ነገ ደግሞ ‘በግቢ’ እንዳይሆን ትላላችሁ፡፡
ስሙኝማ…ዘንድሮ መንደሮች ‘መደብ’ የሚለይባቸው እየሆኑ አይደል…እዛም ለየት ያሉ ‘ቲፎዞነቶች’ ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ ለመደብና! “ዘመድ ከዘመዱ…” ምናምን የሚባል ነገረ አለ አይደል፡፡ ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው አንዱን ጎብኚ እያዟዟረ ኒው ዮርክን ያስጎበኘው ነበር፡፡ እናላችሁ… አንድ ቤተ መንግሥት የሚያክል መኖሪያ ቤት ይደርሳሉ፡፡
አስጎብኚውም እንዲህ ይላል… “ይህ በኒው ዮርክ እጅግ ሀብታም የሆነው ሰው መኖሪያ ቤት ነው፡፡ አብሳዩ ጀርመናዊት ነች፣ የቤት ሠራተኛዋ ፈረንሳዊት ነች፣ ዕቃ አመላላሹ ጃፓናዊ ነው፣ ሜካኒኩ ስኮትላንዳዊ ነው፣ የቤት ጽዳት ሠራተኛዋ ስዊድናዊት ነች፣  ፀሀፊው ደግሞ አሜሪካዊት ነች፡፡”ጎብኚው ሲመልስ ምን አለ መሰላችሁ… “ይሀ መኖሪያ ቤት ሳይሆን የዓለም ፍርድ ቤት ነው፡፡” ኧረ እዚህ በመጣ፣ ቤተ መንግሥት ሊያስንቁ ምንም የማይቀራቸው ቤቶች ባይኖሩ ነው! እንደውም አንዳንዶቹ እንዲህ አይነት ቤቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሲያልፉ የመኪና ጥሩምባ ማሰማት ክልክል እንደሆነ በቀደም ወዳጄ እየነገረኝ ነበር፡፡ “ገና ምን አይተሽ!” አለ ባል ሚስት ላይ ሲፎክር!
እኔ የምለው…እግረ መንገዴን…ደግሞ የት አካባቢ ነው…“ከጥራት በታች የተሠራ መንገድ እየፈረሰ ነው…” ምናምን ሲባል ሰማን ልበል! …‘ማፍረስ’ ቀላል የሆነባት አገር! ሀሳብ አለን… ለማፍረስ ጥቅም ላይ የሚውሉ ዲጂኖ ምናምን አይነት መሣሪያዎች ከውጪ ይገቡ እንደሆነም፣ እዚሁ ይመረቱ እንደሆነም ብዛታቸው ይቀነስልንማ! አሀ…ችግር የሚፈጥርው እኮ ‘እንደ ልብ’ የሚገኝ ነገር ነው፡፡ ለነገሩ ዲጂኖውም ቢጠፋ… አለ አይደል… “በጥፍሬ እየቧጠጥሁ ካላፈረስኵ ሞቼ እገኛለሁ…” የምንል አንጠፋም፡፡ ዘመኑ እንዲህ ነዋ!
እናላችሁ…‘የቲፎዞነት’ ዘመን ነው፡፡ እኛ “የለም…” የተባልነው የለስላሳ መጠጥ አይነት እዛው በዛው ለ‘ቲፎዞ’ ሲሰጥ ያየንበት ሬስቶራንት ነገር አለ፡፡
ታዲያላችሁ…በየስብሰባውም የሚገጥማችሁ ነገር ‘የቲፎዞ’ ነገር ነው፡፡ ያው ያቺ ከድሮ ጀምሮ የተለመደች ‘በተንተን ብሎ የመቀመጥ’ ስትራቴጂ አለች አይደል… ሰበሳቢውም “አንድ ከዚህ ጫፍ፣ አንድ ከመሀል፣ አንድ ከወዲያኛው ጫፍ…” ምናምን ይልና ስትራቴጂያዊ ቦታቸውን የያዙ ‘የቲፎዞ ስብስቦች’ ….ይቆጣጠሩታል፡፡
እናላችሁ…ሰዉ ከሁሉ አስቀድሞ “እንትን መሥሪያ ቤት ሰው ታውቃለህ…” ምናምን የሚባለው ዘመኑ ‘የቲፎዞ’ ስለሆነ ነው፡፡
አሁን፣ አሁን የሆነ ነገር፣ በተለይ የጥበብ ሥራ፣ ሲያደንቁልን ከሥራው ይልቅ “ሰውዬዋ ፕሮፓጋንዳ እየነሰነሰች ነው እንዴ!” እንላለን፡፡
እናማ…“ሙሽራን ያላችሁ እስቲ እንያችሁ…” አይነት የመጠቃቀስ፣ በምስጢር የመጠራራት ‘ቲፎዞነት’… አለ አይደል… ‘በጨው ደንደስ በርበሬውን እያስወደሰ’ ስለሆነ ጦሳችንን ይዞ ይሂድልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ከአበባው መላኩ ጋር ስለጐንደርና ስለ ጉዋሳ የተጨዋወትነው

“ከግጥም ከመሰንቆ ልጆች ጋር እንዴት ተዋወቃችሁ?” አልኩት፡፡
“ግጥም በመሠንቆዎች ስለ ፓኤቲክ ጃዝ የሚያውቁት ነገር የአለ መሰለኝ፡፡ ወርሃዊውን ዝግጅት የመካፈል ልማድ እንዳላቸው ነግረውናል፡፡ በመጀመሪያ የሰማሁት የግጥም በመሰንቆ ቡድኖች ለግጥም በጃዝ ስጦታ ለመስጠት ይፈልጋሉ - ነው፡፡ በ3ኛ ዓመት ዝግጅት ሰዓት ሳይሆን መድረክ መስጠት ይቻላል…ከጐንደር ድረስ መጥተው፣ የጐንደርን ስም ጠቅሰው እንዴት ብለው ይመለሳሉ? ሌላም የሽልማት ፕሮግራም አለንና ያንን መጠቀም ይችላሉ አልን፡፡ መጡ ተገኙ ነገር ግን በራሳቸው ምክንያት ስጦታውን ሊያከናውኑ አልቻሉም” አለኝ፡፡ እኔ የጐንደሮቹን ግጥም በመሰንቆ ቡድኖች ጠይቄያቸው ቴክኒካል ችግር ለሁኔታው አለመመቻቸት ምክንያት ሆኗል ነው ያሉኝ፡፡ ዞሮ ዞሮ ስጦታው በበረከት በኩል እንዲደርሳቸው አድርገናል ነው ያሉት፡፡ መንፈስ ለመንፈስ ግን ተግባብተዋል ብዬ ዘለልኩት፡፡
“ዋናው ነገር ተገናኝተናል፡፡ መስከረም ላይ እኔን ጋበዙኝ፡፡ በረከትን ጠየኩት “ለግጥም የተሰጡ ልጆች ናቸው” አለኝ፡፡ “የግጥም አገልጋዮች ናቸው” አለኝ፤ አለ አበባው፡፡
የግጥም ዲያቆናት፣ ምዕመናን - ማለቱ ነው፡፡
“ወጪያችንን ችለን ለምን እንደግሩፕ አንሄድም?” ተባባልንና ሁላችንም የፓኤቲክ ጃዝ አባላት ሄድን፡፡ አንዳንዶቹ ጐንደርን አይተው ስለማያውቁ ደስ አላቸው፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ የምናውቀው እኔ በ98 አውቀዋለሁ ግሩሜም ያቀዋል - ምሥራቅና ምህረት ናቸው የማያውቁት፡፡ አቀባበላቸው ግሩም ነበር! በጣም ደስ ብሏቸው ነበር…ግጥም ንባቡን በዋናነት እኔ ደጋገምኩ እንጂ ሁላችንም አቅርበናል! አዳራሹ ግጥም ብሎ ነበር! ብዙ ህዝብ ነበር፡፡ የቆመው ከተቀመጠው ይበልጥ ነበር! እኔ እንደዚህ አልጠበኩም፡፡ በአውሮፕላን ችግር ፕሮግራም ተሰርዞ፣ ባዲስ መልክ አዘጋጅተውት ያለቀኑ ተዋውቆ በፌስቡክ፣ በአንዳንድ ቦታ ብቻ አስተዋውቀውት ነው፡፡ ብዙ ሰው መጣ! እነሱም ተደምመው ነበር፡፡ በጣም መልካሙ ነገር ጥሩ የሚሰሙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ያየነውንም ትዝብት ተናገርን ጐንደርን ያህል አገር ይዘው፣ በውስጡ ያለውን ታሪክ፣ ላለፉት 250 ዓመት ዘመን ላይ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ትምህርት፣ የአስተዳደር መዲና የሆነች አገር ይዘው ያን ያን እሚሸት ነገር የሌለበት ነገር ትርፉ  ድካም ነው፡፡ ዘጥ ዘጥ ነው፡፡ ዞር ዞር በሉ - ወላጆቻችሁን ጠይቁ፡፡ ወደአቅራቢያችሁ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ጐራ በሉ - መዛግብቱን እዩ፡፡ መዛግብቱ ምን ይላሉ፡፡ በዚያ መጠን ሥሩ፡፡ ታላላቆቻችሁን ጋብዙ - ከዚያ ምን ተገኘ የሚለውን እዩ!...መከርን፣ ሸጋ ነው!
“የባህል ቤቱን እንዴት አገኛችሁት?”
“…ዘመናዊውን ዘፈን እንኳ ወዝ ይሰጡታል፡፡ ሐማሌሌን እንኳ አሳምረው ነው የሚዘፍኑት፡፡ ሕብረ - ብሔራዊ ስሜት አላቸው፡፡ የሁሉ እናት የመሆን ስሜት ነው ያላቸው!... በጣም ቆንጆ ነው! ሴቶች ድራም ይዘው ማየት በጣም ትፍስህት ሰጥቶኛል፡፡ የመጨረሻ ሙድ አለ፡፡ የግጥሞቹ ይዘት ላይ እኔ ትንሽ ያዝ አድርጐኛል! ስሞች እያነሳች ታወድሳለች! ቀረርቶ ሽለላዋ መልካም ነው - ሌላው ግን የሥነ - ቃሉ የግጥሙ ባለቤቶች ሆነው ምንም አዳዲስ ይዘት የላቸውም ወይ? ብያለሁ!” አለኝ፡፡
“የስቴጅ ግጥም አንባቢዎችንስ ብስለት ነገር እንዴት አየኸው?”
“ከ12 ዓመት በፊት ፑሽኪን አዳራሽ ይቀርቡ የነበሩ ግጥሞች ነበሩ! በወጣቶች፣ በሁሉም አቅጣጫ ወጣት ናቸው! ነጠላ ሀሳብ ላይ የማተኮር ችግር አያለሁ! ያንን ጊዜ ያስታውሰኛል፡፡ የተወሰኑ ተስፋ የሚጣልባቸው ነበሩ - በተለይ የዕይታ ነገርን ያበሰሉ ገጥመውኛል…የመለመልነውም ልጅ አለ - ከውስጣቸው፡፡ ልሣን ይባላል፡፡ Talent Hunt ነው፡፡
ከየቦታው ለፓኤቲክ ጃስ ከምነመለምላቸው ለምሣሌ ከወሎ አካባቢ ሼህ ቡሽራ የሚባሉ ናቸው መንዙማ አዋቂ ጋብዘን ሆቴላቸውን አበላቸውን ችለን ነበር - ሌላ መንግሥቱ ዘገየ” ቀብድ የበላች አገር” የሚል መጽሐፍ የፃፈ ነበር - መጽሐፉን አይተን በአድራሻ አገኘነው! እሱንም ቀለቡን ችለን ጋብዘናል! ሀሳቦች አሉን፡፡ ለምሳሌ ደብረዘይት አካባቢ ቶራ ቡላ የሚባል የሥ/ጽሑፍ ማህበር ነበር፡፡ እነሱም እንዲያቀርቡ አስበን ነበር፡፡ እነ ምንተስኖት ማሞን የደብረዘይቶቹን ነግረን ነበር፡፡ ወደ አዋሳ አካባቢም “60 ሻማ” እሚባል ማህበር ነበር፡፡ ይሄ ሃሳብ እያለ ነው እንግዲህ ጐንደሮች ሲጠሩን የሄድነው! እንደነሱ በአውሮፕላን ባይሆን በመኪና ነው!”
በበኩሌ አልኩት፤ “የናንተ አዳራሽ - የእኔ ኦፕን - ኤር ነው! ልዩነቱ ያ ነበር፡፡”
የጉዋሣ ነገር
በረዶ አገር ሄጄ አቃለሁ - አውሮፓ፡፡ እንደ ጉዋሣ ያለ ቀዝቃዛ ቦታ በህይወቴ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ በነገራችን ላይ ዘፈኑ ግጥም ላይ
“አገሯ ዋሳ መገና፤ አገሯ ዋሳ መገና
ምነው አልሰማ አለች፣ ብጣራ ብጣራ”
“ዋሣ” ይመስለን የነበረው “ጉዋሣ” ነው፡፡ “መገና”ም የመሰለን “መገራ” መሆኑን ልብ እንበል፡፡
ከአዲሳባ ለተነሳ ሰው ወደ ደብረ ብርሃን ይኬድና፤ ጉዶ በረትን አልፎ ወደ ደብረ ሲና አምርቶ (ደብረሲና እንግዲህ ዳኛቸው ወርቁ በአደፍርሱ “እግዜር አገሮች ሰርቶ ሰርቶ የተረፈውን ኮተት ያከተባት ከተማ” ያላት ናት) ጣርማ በር ጋ ሲደረስ ወደ ግራ እጥፍ ነው፡፡ 180 ኪ.ሜ ላይ ማለት ነው፡፡ መዘዞና ባሽ ይቀጥላል፡፡ ወደ ግራ ቢሉ ሞላሌ አለ፡፡ ቀጥታውን ሲኬድና ሲቀጠል ግን ይጋም (Yigam) ይገኛል፡፡ ይጋምን ሲያልፉ ጉዋሣ አጥቢያ ይደርሷል፡፡ በዚያ ወደቀኝ ወደ ካድሉ ወደ አጣዬ ያስኬዳል፡፡ ግራ ግራውን ማህል ሜዳ እንግዲህ ዙሪያ ገባውን አለ፡፡ በማህል ሜዳ ተሻግሮ ወደ ግሼ ይዘለቃል፡፡ እኛ ግን ወደ ማህል ሜዳ ስንሄድ ሰፌድ - ሜዳን አልፈን ነው፡፡
ይሄ ሙሉቀን የዘፈነለት ጉዋሣ ለአዲሳባ ሰሜን ነው፡፡ የቅዝቃዜውን ነገር አለማንሳት ነው፡፡ ከባህር ወለል በላይ ከ3200 -3700 ሜትር ከፍታ ላይ ነው፡፡ የተሰባበረ ተራራ ይታያል፡፡
ፀጋዬ ገ/መድህን “በአንኮበር” ግጥሙ “የፈፋ አነባበሮ” ያለው ነው፡፡
ወደ ምዕራብ የሚጓዙና ሰንጥቀውት የሚያልፉ ስምጥ ሸለቆዎችና የባህር ሸለቆዎች አሉ፡፡ በአባይና በአዋሽ ማህል ያለ ውሃ ማገቻ ነው፤ ቢባል ድፍረት አይሆንም፡፡ የጉዋሣ ምሥራቃዊ ወገን ተረተሩን ቁልቁል ወደሸለቆው ልኮ ታላቁን ስምጥ ገደል ድንገት ሲተረትር ከመነሻው ይርቃል፡፡ ከፍታው መርገብ ይጀምራል፡፡ በ50 ኪ.ሜ ርቀት ውስጥ በ2600ሜ ዝቅታ ደረጃ ባንዴ ውርድ የሚል ታምረኛ ሥፍራ ነው፡፡ ከዚያ ወደ አዋሽ ግርጌ ወርዶ የታላቁን ስምጥ ሸለቆ ወለል ይቀላቀላል፡፡ የጉዋሣ ምዕራብ ደግሞ በድልዳላዊ አካሄድ ወደማህል ሜዳ ይገባል (3000 ሜትር ግድም) መልክዐ - ምድሩና ሠፈሩ እንግዲህ ይሄ ነው፡፡
ከጉዋሣ የግቻ ሣር (Afro alpine) [በአፍሪካ የራሳችን የሣር - ዝርያ ነው] እና በተራራው ትዕይንት መካከል የጉዋሣ ማህበረሰብ ሎጅ (ማረፊያ - መናፈሻ) አለ፡፡ ለዚያ ቦታ እንደወፍ ጐጆ ማለት ነው፡፡ ክፍሎቹ፤ በትልቅ ቅጽ ተገነቡ እንጂ በልማዳዊ መንገድ የተሠሩ የወፍ ጐጆዎች ማለት ናቸው፡፡ የጉዋሣ ማህበረሰብ ነው የሚያስተዳድራቸው፡፡ አራት ባላመንታ - አልጋ ክፍሎች (“ጭላዳ”፣ “ቅልጥም - ሰባሪ”፣ ቀይ ቀበሮ” የሚባሉ የከፋ ቀን በአገሩ በሚገኙት ብርቅዬ እንስሳት የተሰየሙ) አይቻለሁ፡፡ ከኒህ በተለየ፣ የእሳት መሞቂያን ያካተተ እልፍኝ፤ ምግብ - ቤትና ማድቤት ያለው ትልቅ የእንግዳ  ማረፊያ ክፍል አለ፡፡ የትምህርትና የመረጃ ማዕከል ባንድ ወገን ያለ ሲሆን፤ የመታጠቢያና መፀዳጃ ያለው ዘርፍ - ክፍልም አለ፡፡ ለካምፕ አመቺ ቦታ አለው፡፡ የገዛ ድንኳን ይዞ አሊያም ከማህበረሰቡ ቱሪዝም ማህበር ተከራይቶ ደንኩኖ መሥፈር ይቻላል፡፡ ሰው የገዛ ምግቡን ሸክፎ መምጣት እንዳለበት መቼም ግልጽ ነው፡፡
የጉዋሣ ማህበረሰብ አካባቢ ጥበቃ አጥቢያ በመኪና መንገድ የሚደረስበት ነው፡፡ ከአዲሳባ ማህል ሜዳ በሚሄደው ህዝብ ማመላለሻ ሽር ማለት ይቻላል፡፡
ጉዟችን መጀመሪያ ከደብረ - ብርሃን 15 ኪ.ሜ የምትገኘው “አማፂዎቹ” የተባለ ቦታ ቁርስ በመብላት እንደሚጀምር የጉዞ - መሪያችን አብስሮናል፡፡ “አማፂዎቹ”ን ለማወቅ መቼም ከስማቸው መረዳት ነው ዋናው” ነው ያለን ጉዞ መሪው፡፡ በኋላ የደረስነው አንድ ጉብታጋ ነው፡፡ ከዚያ ሆነው ቁልቁል ሲያዩ የሚያምር መልክዓ ምድራዊ ትርዒት አለ፡፡ የኢትዮጵያ አብያተ - ክርስቲያናትና ቤተ - መንግሥቶች ለምን ከፍታ ላይ እንደሚሠሩ ተወያየን፡፡ ከፍታ አንድም ለማየት አንድም ለመታየት ነው - ተባባልን፡፡
ከዚያ እንግዲህ ጣርማ - በር ላይ ታጥፈን ማረፊያ - መናፈሻው (Lodge) ጋ ደረስን፡፡ ምሣ በላን፡፡
ከዚህ ወዲያ ነው ጉዱ! የእግር ጉዞ ተጀመረ፡፡ የእግር ጉዞ ታሪክ አስረጂ አጠገባችን አለ፡፡ እኔ ብዙም ሳልራመድ ዳገቱ ያደክመኝ ገባ፡፡ አንዴ አረፍኩ፡፡ ትንሽ ሄጄ ልቤ ያለልክ ትመታ ጀመር፡፡ “በቅሎ ቢመጣልኝ ይሻላል” አልኩ፡፡ መቼም ከተሜዎች ናቸውና መድከማቸው አይቀርም ብለው ነው መሰል፣ አገሬው በቅሎ እየነዳ ይከተለናል፡፡
አንዷን በቅሎ አመጡልኝ፡፡ በበቅሎ ተጉዤ አላውቅም፡፡ እንዴት ልውጣ? ወደ አንድ ከፍ ያለ አፋፍ በቅሎዋን አስጠጉልኝና ተደጋግፌ ወጣሁ፡፡ በቅሎዋን የሚስቡልኝ አንድ አጭር ቆፍጣና አዛውንት ናቸው፡፡ ነገረ- ዕንቆቅልሹ ገረመኝ፡፡ እኒህ የ81 ዓመት ሽማግሌ መንገዱን እንደወጣት ይሸነሽኑታል፡፡ እኔ ደግሞ ከሳቸው በጣም በዕድሜ የማንሰው ዘመኔኛ በቅሎ ላይ ነኝ! የበቅሎ አነዳድ መመሪያ ተሰጠኝ:-
ዳገት ሲሆን ወደ ኮርቻው ቀዳማይ ድፍት!
ቁልቁለት ሲሆን ወደኋላ ልጥጥ ማለት!
“ቁልቁል መሳብ፣ ሽቅብ መሳብ” እንዳለው ደራሲው፤ ወጣነው፡፡ ወረድነው፡፡ አሥራ ሰባቱን ኪሎ ሜትር ተጓዝነው!
መኪናችን ዕቃችንን ሸክፎ ቀድሞን ደርሷል፡፡ ቀድመው ለጥናት የመጡ ፈረንጆች እዚሁ ግድም መሥፈራቸውን ምልክት አየን፡፡
ሰው ሁሉ ደረስን ብሎ እፎይ ማለት ሲቃጣው፤ “ፍራሽና አንዳንድ የመኝታ ዕቃ ይዛችሁ ሽቅብ ውጡ፤ መድረሻችን ገና ነው” ተባለ፡፡ ያዳሜ ወሽመጥ ቁርጥ አለ! እዚሁ አይቀር ነገር ሁሉም አንዳንድ ፍራሽና የመኝታ ዕቃ እየያዘ ዳገቱን ተያያዘው፡፡ እንዳይደረስ የለም ተደረሰ፡፡ እኔ ሙላዬ ተላቋል፡፡ ብሽሽቴ ቀልቷል!
ካምፕፋየር ሊደረግ እሳት ተያያዘ፡፡ ፍልጥ ተደመረ፡፡ ነደደ፡፡ ሙቀት መጣ፡፡
ጉሙን ግን ማን በግሮት፡፡ አርድ አንቀጥቅጥ ነው፡፡ አገሬው አሁንም ዕቃ ያመላልሳል፡፡ ብርዱ -10 (ኔጋቲቭ 10) ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው፡፡
ስለ ጉዋሣ ለማወቅ አፈ - ታሪካዊ ትውፊቱን አንብቤያለሁ፡፡
እንደቀበሊኛው አፈ ታሪክ ከሆነ ጉዋሣ የተፈጠረው አንድ መነኩሴ ከተራገሙ በኋላ ነው፤ ብሎ ይጀምራል፡፡ በዚያን ጊዜ ይህ ቦታ እጅግ የበለፀገ የግብርና ቦታ ነበር ይባላል፡፡ በጣም ምርጥ የተባለ ጤፍ ይመረትበት ነበር፡፡ አንድ መልካምና ብልህ የሆኑ አቼ ዮሐንስ የተባሉ መነኩሴ እዚያ ቦታ ይኖሩ ነበር፡፡ ሥራቸውን በሚገባ እያከናወኑ መሬቱንም ባርከውት ነበር፡፡ ሆኖም አንዲት ሴት ከመነኩሴው ልጅ ፀንሻለሁ ብላ በማውራቷ በመነኩሴውና በአገሬው ፊት አረጋግጪ ተብላ ሸንጐ ፊት ቀረበች፡፡
“ዋሽቼ ከሆነ ድንጋይ ያድርገኝ” ስትል ማለች፡፡
ወዲያውኑ ወደ ድንጋይ ተቀየረች፡፡ መነኩሴው ግን በዚህ ብቻ አልረኩም፡፡ ሰው እሷን በማመኑም በጣም ቅር ተሰኙ፡፡ ስለዚህም ያንን ቦታ
“አንተ ቦታ ከእንግዲህ የተረገምክ ሁን!! የመጨረሻ ቀዝቃዛና ጨፍጋጋ ሁን!! የበለፀገው የግብርና ምርትህም ከእንግዲህ ግቻ ይሁን!!” ብለው ረገሙት፡፡ ይህን ሲሉ ወዲያው የአካባቢው አየር ተለወጠ፡፡ መሬቱም ዛሬ የሚታየው የጉዋሣ ቦታ ሆነ፡፡ አፍሮ አልፓይን የሣር ዘር መሆኑ ነው፡፡ ያ መርገምት መንደሩን ደሀ አደረገው፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ያገር ሽማግሌዎች ይቅርታ ብንጠይቅ ይሻላል ተባባሉ፡፡ እኒያን መነኩሴም ፍለጋ ያልሄዱበት ቦታ የለም፡፡ ሆኖም መነኩሴው ከረዥም ጊዜ በፊት አርፈው ኖሯል፡፡ ሰዎቹ ግን አፅማቸውንም ቢሆን መፈለግ አለብን ብለው ፍለጋቸውን ቀጠሉ፡፡ የመነኩሴው መንፈስ ቢታደገን እንኳ ብለው በአጥቢያቸው አፅማቸውን ሊያሣርፉ አስበው ነው፡፡ አፅማቸው ተገኘና ፍሩክታ ኪዳነ ምህረት ዳግመኛ ተቀበሩ፡፡ ለሠራኸው ጥፋት የምትከፍለው ብዙ ነው! መንፈሣዊ ፀጋ ድህነትን ለማሸነፍ አስፈላጊ ነው!
ሰዎቹ ራሳቸውን በመውቀስ የድህነታችን ዕንቆቅልሽ ታሪኩ ይሄ ነው ይላሉ፡፡     
እንግዲህ ከአበባው ጋር ወደ ጓሣ አብረን ሄደናል፡፡ “ስማ፤” አልኩት፡፡ እርግጥ ካንተ የምለየው፤ እኔ ጉራጌ አገር ዘሙቴ ማርያም ነበርኩ፤ ከዚያ ጐንደር ከዚያ ጓሣ መሄዴ ነው! የእኔ የጓሣ አመለካከት አለ ያንተስ? አልኩና ጠየኩት፡፡
“እኔ የሀረር ሰው ነኝ - ደጋ አደለም - ቆላ ነው - የሚስማማኝም ቆላ ነው!
ከመሄዳችን በፊት የተሰጡኝን ማስገንዘቢያዎች አንብቤአለሁ! አለባበስ -የእጅ ጓንት ወዘተ ያንን ማሳሰቢያ በአክብሮት ካነበቡት አንዱ እኔ ነኝ! እኔ ብርድ በኃይል እፈራለሁ - ለምን እንደሆነ አላውቅም! መድረስ አይቀርም ደረስኩ፡፡ ከከፍታ በላይ ከፍታ ላይ አስደንጋጭ ቪው ነው ያየሁት! ዓለምን በተዛማጅ ከፍታ ማየታችን እየተፈታልኝ ነው የተጓዝኩት - ደስ ብሎኛል፡፡
ቦታው አስደናቂ እንደሆነብኝ ጓሤዎችም አስደንግጠውኛል! ሰው መውደዳቸውና ትህትናቸው! ሁለተኛ እርስ በርስ ያላቸው መግባባትና መከባበር! በተፈጥሮአችን እኛ ከተሜዎቹ እራሳችንን እንለይና የበዛብን ሲመስለን በጣም አጉረምራሚዎችና ተናዳጆች፤ በተለመደው መከባበር፣ ጠባይ ውስጥ አደለም ሥራችንን የምናከናውነው! ብሶተኛ ይበዛል - ፉከራው ይበዛል! ያ ነገር እዚያ የለም! ሸክም ተሸክመው በቅንነት ይኖራሉ እነሱ! ሰዎችን ለማገልገል፣ ለመርዳት ያላቸው ጉጉት፤ መመራመር ሳያስፈልግ እነሱ ተፈጥሮን ተገዳድረውታል ብዬ እላለሁ! ሠርፀው ገብተዋል፡፡ በቅሎ ላይ መውጣቴ፤ በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በቅሎ ላይ የወጣሁትና፤ ደስ ብሎኛል! ለመጀመሪያ ጊዜም ነው 3700 ከፍታ ላይ የወጣሁት እዚህ ስገኝ!
በቅሎ ላይ መውጣቴ ጥቅሙ በእግሬ እንቅፋት እያየሁ መሄዴ ቀረና በቅሎ ላይ ሆኜ አካባቢውን አያለሁ፡፡ ዞር ስልም የጓደኞቼ ቅፍለት በጉም ውስጥ የሚጓዙ ከሌላ ፕላኔት ድንገት የተከሰተ ስዕል ይመስላል፡፡ በቅሎ ላይ ሆነን ቁልቁለት ወገብ መለመጥ፣ ዳገት ማቀርቀር ነው ዘዴው፡፡ የበቅሎ ጉዞ ስርዓቱ! ወሳኝ መመሪያ! ላለመውደቅ ለማሸነፍ ለመድረስ! የህይወት ልምድ ተመክሮ ነው!
መቼም ውቴል የሚባል ነገር የለም፡፡ እንግዳነታችን ለተፈጥሮ ነው፡፡ የሚያስተካክለንም ተፈጥሮ ነው፡፡ በተፈጥሮ ዳገት ላይ ጉምና ብርድ ለብሶ ለማደር መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
አንድ ሁለቴ ውሃ ተጐንጭቻለሁ፡፡ በቅሎዋ ላይ ሆኜ ጉም ግን እየዳበሰኝ ያልፍ ነበር፡፡ ጢሜ እርጥበት ጤዛ አለው፡፡ ገርሞኝ አገሬውን ጠየኩ፡፡ “ይህ የጉም ሽንት ነው አሉኝ!” ጉሙ ሸናብኝ መቀበል አለብኝ! ይሄ የመጀመያዬ ቀዝቃዛ አገር ነው” አለኝ፡፡
“የእኔ የአውሮፓ ልምድ ይለያል፡፡ መኪናው በረዶ ለብሶ ባካፋ ይዛቃል፡፡ ትልቁ ልዩነት እዚያ ቤት ስትገባ ባየር ማረጋጊያ ሙቅ አየር አለ፡፡ ኮትህን ማውለቅ ይጠበቅብሃል፡፡
ሁሉንም አንድ ላይ እናስበው፡፡ ከNTOው ገላጭ ሌላ አገሬውም ይግለጥልን፡፡ እኔን የመሩኝ ሰውዬ “ነዶና ሰው ተጣላ፤ አዝመራው እምቢ አለ” አሉኝ፡፡
ሌላ እንደኔ ገርሞህ ከሆነ ህፃናትና ሴቶች አላየንም (ውሻም አላየንም ብዬ ነበር) የህብረተሰቡ Pillar የሚባሉትን ሁለት አካላት ህፃንና እናት አላየንም፡፡ ለምሣሌ ዘሙቴ ማርያም ስሄድ ግብዳ ግብዳ ሻንጣችንን ጩጬ ጩጩ ልጆች ናቸው አንከብክበው ዳገት ቁልቁለቱን ፉት ያሉት! ምናልባት ማህል ሜዳ እሚባለውጋ ገብተን ባለመሆኑ ሊሆን ይችላል! ወንድ ይበዛል - ምናልባት ሴቶችና ልጆች እንዴት ነበር ልናገኝ እንችል የነበረው? ቆይ አዘጋጁን እጠይቀዋለሁ፡፡ ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ ሽማግሌዎች በቅሎ መሳባቸው ገርሞኛል፡፡ እኔ በቅሎ ላይ ሆኜ ስጠይቃቸው ዞርም ቀናም ሳይሉ፣ ወግ ባይን ይገባል ሳይሉ፤ መልስ እየሰጡኝ ወደፊት ይገሰግሣሉ በቃ! ተፈጥሮን እኔ አደንቃለሁ፡፡ ለነሱ ተፈጥሮ ተፈጥሮ ነው በቃ! የኑስ የተባለው መንገድ ገላጫችን ያስረዳን የፀሐይ መውጣት መግባት ለነዚህ ሰዎች ጉዳይ አደለም፡፡ ስለ ኢሮብ ሰዎች ስለአዲግራት ሳወራቸው ነበር መኪና ውስጥ ሆነን፡፡ ኢሮቦች ምን ይላሉ መሰለህ “አናንተ ከደርግ ሸሽታችሁ ለመጠለልና ለመዋጋት ነው እዚህ የምትመጡት፡፡ እኛ ግን እንኖርበታለን፡፡ ኑሯችን ይሄው ነው!”
እዚህ አገር ጅቡ እንዳንተ አገር እንደ ሐረር ለትርዒት አይታይም፡፡ ጉልበተኛና ከመጣ የማይመለስ ነው አሉ! ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቅልጥም - ሰባሪ፣ ቀይ ቀበሮ እንደሚኖርበት ጅብም ጓሣኛ ሆኗል!
ማታ ካምፕ ፋየር አደረግን፡፡ ዘቡ መሣሪያ ይዘናል ሳይል ሽለላ ጀመረ፣ ዋሽንት ነፋ ጣሰው! ቅዝቃዜ መሸነፍ ጀመረ፡፡ ይህ ነገር ቢቀረፅ እንዴት አሪፍ ነበር፡፡ ቆጨኝና “እኛን ዓይነት ሰዎች አምጥታችሁ፣ በጥበብ የማርያም መንገድ ምንም ሊፈጠር እንደሚችል እያወቃችሁ፣ ምንም የዶክመንቴሽን ሥራ አለመሠራቱ በጣም ያሳዝናል፡፡
የመጀመሪያ ትምህርታችሁ ይሁን!” ብዬዋለሁ ለሀላፊው ለኤፍሬም (ኤፍሬም ከበቅሎ ቀድሞ ዳገት አፋፍ የሚወጣ፣ ቁልቁለት ወርዶ ቀድሞ ሜዳውን የሚረግጥ፤ ሰው ደከመኝ ብሎ ሲያርፍ እሱ ድንኳን ተከላና ሸከማ የሚጀምር፣ ቀጭን ትዕዛዝ በትህትና መስጠት የሚችል እንደ ኤስኪሞ ጀቦንቦን የለ ልብስ የለበሰ አምበሳ ኃላፊ ነው!)
ለላው ደግሞ ከአገሬው ጋራ መዋሃድ፣ ገብሱ ከየት እንደሚመጣ ማየት ነበረብን፡፡ እንደገጣሚ ይሰማኛል፡፡ ሰውን ስታውቅ ነው ተፈጥሮ ሙሉ የሚሆነው፤ አልኩኝ በልቤ፡፡ “ሎጁ ላይ ገለፃውን ሳናዳምጥ አቋርጠን መሄዳችን ቅር ብሎኛል” አለ አበባው፡፡ ልጁ፣ ገላጩ ዐረፍተነገሩን እንኳ ሳይጨርስ ነው መንገድ የጀመርነው፡፡ አሰቅቀነዋል - እኛም ሙሉ ሳንሆን ነው መንገድ የጀመርነው ማለት ነው፡፡ ዕውነት የሚመጣው የሰው ትንፋሽ ሲጨመርበት ነው - እኔ በዚህ አምናለሁ - አልኩት፡፡ ጆሮህ ቅላፄ ይናፍቃል - መፃፍ ማለት ያ ነውና! እኔ ቁጭት ነው ያለኝ!...Next time መምጣታችን አይቀርም ግን 1st Impression is last Impression የሚባለውን የሚያክል የለም! ገላጩ ልጅ እንደዛ ተገናኝተን ተዘጋጅቶ ካፉ የሚወጣውን ሳንሰማ ሄድን! ሰውየውን ከነቃናው ከነትንፋሹ ማግኘት ነበረብን፡፡ መግባባት ማለት ያ ነውና! የታሪክ ነጋሪውንም History የሚናገረውን በመንገድ ላይ ሙሉ ነገር አላገኘንም! በዚያም አንፃር ጐሎብናል! እንደወዳጅ ቀርበነው ማውጋት ነበረብን! ያ ጅምላውን ነገር ሙሉ አያደርገውም፡፡ እንደ ጋዜጠኛም እንደ Poetም ይመለከተኛል!…ገበሬው ጋ ችግር እንዳለ በቅሎ ሳቢው ነዶና ሰው ተጣላ ካሉኝ በኋላ የዘይት ዋጋ፣ የጨው ዋጋ የኢኮኖሚ ችግር እያልን ከተማ የምናወራውን From The Horses Mouth ከግብርናው ጌታ ሰማነው፡፡ ዕድገት አለ የለም ያኔ ትወስናለህ!
እንደተመክሮ ድንቅ ነገር ነው! ሪፖርት ሳይሆን ህይወት ሊኖረው ይገባል! ስሜቴን ልቀጥልልህ:-
ጣሰው ስለዋሽንት ቢነግረኝ በጣም ድንቅ ይሆናል! ጠባቂዎቹ እንደወታደር ጠባቂ ነን ብለው አልራቁንም - አብረውን ካምፕ ፋየር አደረጉ፡ የዕውነት ህዝባዊ ስትሆን ልባዊ - ህዝባዊ ነው የምትሆነው! መሣሪያውም፣ እኛም፣ ጠባቂዎቹም፣ ዋሽንቱም…እኩል እሳት የሚሞቅበት ነው ጉዋሣ! ህዝባዊነት፣ ቱሪስትነት፣ የአካባቢ ጥበቃና ጥበብ ሁሉም ማዕቀፋቸው እሳት ነው! እሳት ወይ አበባ እዚህም አለ፡፡ ለዚህ ነው በየፓርኩ ግጥም ይነበብ የሚለው ሃሳብ ትርጉም የሚኖረው! እንደማሳሰቢያ፤ ለአዘጋጆቹ ይህን እላለሁ:-
ቅድመ - ማስገንዘቢያ ቢኖር፡፡ ከከባዱ ወደ ቀላሉ ከመሄድ ለአፍቃሬ - ግጥሙ የፓኤቲክ ጃዝ ተከታታይ ከቀላሉ ወደ ውስብስቡ ቢኬድ (Law of dialectics)፡፡ ብቁ ዶክመንቴሽን (ምስለ - ዘገባ) ቢኖር፡፡ የማህበረሰቡ ተሳትፎ በቂ ቦታ ቢያገኝ፡፡ የማህበረሰቡ ክህሎት ተጠንቶ ከገጣሚያኑ ቢዋሃድ፡፡ ከተፈጥሮ ጋር መጣረርም ኅብር - መፍጠርም የጥበብ አካል መሆኑ ልብ ቢባል፡፡ የቴክኖሎጂ ግብዓት ከተፈጥሮው ሁኔታ ጋር መጣጣሙ ቢታሰብበት የተሻለ ታሪክ የመዘገብ አቅም ይኖረናል!


Published in ባህል
Page 2 of 19