ከ120 በላይ ኢትዮጵያውያን ከሊቢያ ይመለሳሉ

እስራኤል ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 60ሺህ የሚጠጉ አፍሪካውያን ስደተኞችን ከሃገሯ እንደምታስወጣ ያስታወቀች ሲሆን በህገወጥ መንገድ በሊቢያ የሚኖሩ ከ120 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ወደ ሃገራቸው ይመለሳሉ ተብሏል፡፡ የእስራኤል ካቢኔ ባለፈው እሁድ ስደተኞቹን የሚያስወጣ አዲስ ህግ ካፀደቀ በኋላ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያዊን ኔትያሁ፣ ህገወጥ ስደተኞቹን ከሀገራቸው እንደሚያስወጡ አስታውቀዋል፡፡ የአገሪቱ ካቢኔ ባፀደቀው መመሪያ መሰረት እስራኤል በመጀመሪያው ዙር 4ሺ ስደተኞችን የምታስወጣ ሲሆን በቀጣይም በዘላቂነት ህገወጥ ስደተኞች ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ በዘላቂነት ለመከላከል ከግብጽ የምትዋሰንበትን ድንበር ጥበቃ እንደምታጠናክር ገልፃለች፡፡ ከሀገሪቱ ይወጣሉ ተበለው የሚጠበቁት አብዛኞቸ ሱዳናውያንና ኤርትራውያን ሲሆኑ ኢትዮጵውያኑም የገፈቱ ቀማሽ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሊቢያን ማረፊያ ያደረጉ ከ120 በላይ ኢትዮጵያውያን በግብጽ ካይሮ ባለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትብብር የጉዞ ሰነዳቸው ተዘጋጅቶላቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በአለማቀፍ የስደተኞች ተቋም (IOM) ትብብር እንደሚመለሱ ታውቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በባህሬን በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ትሠራ የነበረች ኢትዮጵያዊት በሶስት ወንዶች ተጠልፉ መደፈሯንና በሴተኛ አዳሪነት እንድትሰራ መገደዷን ገልፃ፤ ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለውን ባንግላዲሻዊ እንደከሰሰች ሰሞኑን ተዘግቧል፡፡ የ28 አመቷ ኢትዮጵያዊት ቆሻሻ ለመድፋት ወደ ውጪ ስትወጣ ሁለት ማስክ ያጠለቁ ወንዶች አፍነው በመውሰድ አፓርታማ ቤት ውስጥ ከነበሩ አራት የተለያዩ አገራት ሴቶች ጋር በሴተኛ አዳሪነት እንድትሰራ መደረጓን ገልፃለች፡፡ በቀን አስር ጊዜ ያህል ከተለያዩ ወንዶች ጋር ወሲብ እንድትፈጽም ትገደድ እንደነበርም ለፍ/ቤት አስረድታለች፡፡

Published in ዜና

ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ነበር ያ የፍርሃት ግብታዊ እርምጃ የተወሰደው፡፡
በዚያች እለት ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ 13 ሚኒስትሮች (ምክትሎችን ጨምሮ)፣ 1 የዘውድ ም/ቤት ፕሬዚዳንት፤

ዘጠኝ የጠቅላይ ግዛት እንደራሴዎች፤ 2 የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት፣ 11 የተለያዩ የጦር ኃይሎች እና ፖሊስ

አዛዦች፣ 3 የአውራጃ አስተዳዳሪዎች፣ 7 በልዩ ልዩ ኃላፊነት ላይ የነበሩ (የኢት/ቀ መስቀል ኃላፊውን ጨምሮ) በድምሩ

52 የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ባለሥልጣኖች በዚያች ዕለት ተረሸኑ፡፡
ከነዚሁ ጋር ሌ/ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም (የደርግ ሊ/መንበሩን) ጨምሮ የደርግ እና የንዑስ ደርግ አባላትም፣

በድምራቸው 8 የሆኑ፣ ከ፻ አለቃ እስከ ሻምበል የሚደርሱ መኮንኖች፣ አንድ ወታደር እና አንድ ሲኒየር ቴክኒሺያን

ተገደሉ፡፡ በድምራቸው 60ዎቹ እየተባሉ የሚጠሩት የደርግና የሌሎቹ ግድያ፣ የዚያ ትውልድ አብዮተኞች ጭካኔ

መጀመሪያ የሆነው አረመኔአዊ ተግባር ተፈፀመ - የዛሬ 39 አመት፡፡
ባለሥልጣናቱን የመግደሉን ሐሳብ ቀድሞውኑ የወጡኑት  ወደ አራት የሚያህሉ የደርግ አባላት ነበሩ። ከእነዚህም

መካከል የቻሉትን ያህል ተታኩሰውና ጥለው ለመሞት የበቁት ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም አንዱ ነበሩ፡፡ ሌሎቹ

ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ኮማንደር ለማ ጉተማ እና ዶክተር በረከተ አብ ሃብተሥላሴ ነበሩ፡፡
ይህን የመግደል ምክር ሻለቃ መንግሥቱ ወደ ደርግ አባላት አቀረቡት፡፡ በደርግ አባላት ስብሰባ ላይ ሻለቃ ተስፋዬ

ገ/ኪዳን፣ ሻለቃ ብርሃኑ ባይህ፣ ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሌሎች ጥቂት የደርግ አባላት ተቃወሙት፡፡
ከፍ/ቤት ውጭ የሚደረግ ውሳኔ የመለዮ ለባሹን ድጋፍ ያሳጣናል በማለት ተከራከሩበት፡፡
ነገር ግን የአማን እና የመንግሥቱ ኃይለማርያም የሥልጣን ሽኩቻ የባለሥልጣናቱን ዕድሜ ቀጨው። አማን ሚካኤል

አንዶም ሲገደሉ ለርሳቸው ሞት ማጀቢያ በማድረግ የዚያኑ ዕለት እንዲፈፀም ተደረገ።
በእርግጥም  ጉዳዩ በአግባቡ ሊዳኝ መርማሪ ኮሚሽን የተባለ ኮሚቴ ተቋቁሞ መመልከት ጀምሮ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር

መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶክተር በረከተአብ ኃብተሥላሴ፣ ዶክተር ደሃድ አበቋያ፣ ዶ/ር መኮንን ወ/አማኑኤል፣ አቶ አሰፋ

ሊበን፣ አቶ ዘነበ ኃይሌ፣ አቶ ሁሴን እስማኤል፣ አቶ ጌታቸው ደስታ፣ ኮማንደር ለማ ጉተማ፣ ኮ/ል ነጋሽ ወ/ማካኤል፣

ሻለቃ ዓለማየሁ ሥዩም፣ ሻለቃ አድማሱ ነጋሽ፣ ሻምበል ምትኩ ደምሴ፣ ሻምበል ሰላም ህሩይ፣ እና አቶ መዋዕለ መብራቴ

የነበሩበት ኮሚቴ ነበር በአዋጅ የተቋቋመው። ከኮማንደር ለማ ጉተማ ጀምሮ ያሉት የደርግ አባላት ነበሩ፡፡ ከዚህም ሌላ

ይህንኑ ጉዳይ የሚመለከት የወረዳና የጠ/ፍ/ቤቶች ልዩ የጦር ፍ/ቤት ተቋቁሞ ነበር፡፡ የጦር ፍ/ቤቱ ዳኞች በመሆን

የተሾሙት ኮ/ል ንጉሤ ወ/ሚካኤል፣ ኮማንደር ተስፋዬ ብርሃኑ፣ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ሻለቃ ይልቃል ክንዴ፣

ሻምበል ሰሙ ንጉሥ ሥዩም፣ ሻምበል ቀማቸው ገብሬ ሲኾኑ ዐቃቤ ሕግ በመኾን ደግሞ ኮ/ል ጐሹ ወልዴ ተሰየሙ፡፡

በኋላ ግን በሻለቃ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ፊርማ በአንድ ደብዳቤ ችሎቱ በኢኮኖሚ አሻጥር ላይ ብቻ እንዲያተኩር የሚል

ትእዛዝ ወጣ። መርማሪ ኮሚሽኑም የያዘው ምርመራ እንዲቀዘቅዝ ተደረገ፡፡
ደርግ የንጉሠ ነገሥቱን ባለሥልጣናት ከሐምሌ 1966 ጀምሮ ቀስ በቀስ እየለቀመ በማስገባት ንጉሡን ብቻቸውን

አስቀራቸው፡፡ በመጨረሻ በመስከረም 1967 እሳቸውንም ወደ ማረፊያቸው አወረዳቸው። ከዚያ ጊዜያዊ ወታደራዊ

መንግሥትን ዐወጀ፡፡ የሚያስገርመው በዚህ ዓዋጅ ዐልጋ ወራሹ ካልሆኑም የንጉሡ የልጅ ልጅ ከላይ ንጉሥ ኾነው

እንደሚሾሙም ተገልፆ ነበር፡፡
የመንግሥቱ ኃይለማርያምና የአማን ሚካኤል አንዶም ቅራኔ በዚህ ዓዋጅ ተጀመረ፡፡ ጄኔራሉ ከሕዝብም እንዲካተት

ፈላጊ ነበሩ፡፡ በእነሚካኤል እምሩ ተጠንቶ የቀረበውም የመድኅን መንግሥትም ይህን ያካትት ነበር፡፡
አማን ሚካኤል አንዶም በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት የተወለዱ፣ ጣሊያን የኢትዮጵያን ግዛት አስፍቶ በመያዝ የቅኝ ገዢ

መንግሥትን ባቆመ ጊዜ ከሀገር ተሰድደው በሱዳን ስለ ኢትዮጵያ ነፃነት የታገሉ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። ንጉሠ ነገሥቱ ከሱዳን

በኦሜድላ ሀገራቸው በገቡ ጊዜ አብረው ከነበሩ ወታደሮች አንዱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባል በመኾን

እስከ ከፍተኛ መኮንንነት ደረጃ በመድረስ፣ በተለይ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባደረገችው ውጊያ ጀግንነታቻውን

ያስመሰከሩ እና የተከበሩ ጄኔራል ነበሩ፡፡ ደርግ ሲነሳ በጄኔራል ማዕረግ በወታደሩና በባለሥልጣናቱ ዘንድ የታወቁና

የተከበሩ የጦር መሪ ሆኑ፡፡ በአገርና በውጭ መኮንንነት ከፍተኛ ትምሕርቶችን የተማሩ ሲኾኑ በመከላከያ ሠራዊት

በተለያዩ ኃላፊነት ተመድበው አገልግለዋል፡፡ በአመራራቸው እና በውትድርናቸው የተደነቁም ነበሩ፡፡ የቃኘው ሻለቃ

የኮሪያ ዘማቹ አዛዥ በምድር ጦርም በተለያዩ የአዛዥነት ቦታ ተመድበው ሠርተዋል፡፡
መስከረም 2 ቀን1967 የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ሀገሪቱን እንደሚመራ፣ ሲታወጅ ልዑል አልጋ ወራሽ፣ እሳቸውም

ካልፈለጉም ልጃቸው ልዑል ዘርዓ ያዕቆብ እንደሚነግሡ ቢገለጽም፣ ንጉሠ ነገሥቱን ከሥልጣን ካወረዱ በኋላ ሀገሪቱን

እንዲመሩ የተደረጉት እኚኹ ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ነበሩ፡፡
ጄኔራሉ ግን የደርግ አባላቱ በተለይም ዋነኛው ተዋናይ መንግሥቱ ኃይለማርያምን አልወደዷቸውም። ከደርግ አባላት

መካከል አጥናፉ አባተ፣ ብርሃኑ ባይህ፣ ሲሳይ ሃብቴ፣ ሞገስ ወልደሚካኤል፣ ዓለማየሁ ኃይሌና በዕውቀቱ ካሣ የተባሉት

የራሳቸው ቡድን በመፍጠር፣ ከደርግ ውጭ ተመካክረው የወሰኑትን የመንግሥቱ ኃይለማርያምን አንደበተ ርቱዕነት

በመጠቀም ያስፈጽሙ ነበር፡፡
ከጄኔራል አማን ሚካኤል ጋርም የሐሳብ ልዩነት መጣ፡፡ “መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጄኔራሉ ናቁን የሚል መንፈስ ያደረበት

ይመስለኛል፣” በማለት ጀኔራል ውብሸት ደሴ ይናገራሉ፡፡ ጄኔራል ውብሸት በጊዜው ከኤርትራው ኃይል ተወክለው

የደርግ አባል የነበሩትና ከአማን ሚካኤል አንዶም ጋር ወደ ኤርትራ በመጓዝ የነበረውን የእርስበርስ ጦርነት ሁኔታ

እንዲያጠኑ፣ ሕዝቡንና ጦሩንም አማክረው መፍትሔውን እንዲያቀርቡ ተልከው ከነበሩት አንዱ ናቸው፡፡ (ምስክርነት፣

ተስፋዬ ርስቴ፣ ግንቦት 2001፣ ገጽ 52)
የኤርትራው ጉብኝት የተደረገው በጥቅምት ወር 1967 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚያ የሥራ ጉብኝት ጄኔራል አማን አንዶም

ሚካኤል “ሕዝቡን በየሰፈሩ፣ ጦሩን በየጦር መደቡ ገብተው አነጋግረዋል፡፡” (ዝ.ከ. ገጽ 52)
የእርስ በርስ ጦርነቱ በውይይት ተፈትቶ ሰላም እንዲወርድ መንገድ መጥረግ እንደጀመሩ የመሰከሩት ጄ/ል ውብሸት ደሴ፤

በሥራ ጉብኝቱ ፍጻሜ ላይ ሕዝቡን በአሥመራ ሣባ ስታዲየም ሰብስበው በትግርኛ፣ በአማርኛና በዐረብኛ የሰላም

መልእክተኛ መሆናቸውን እንደገለጹም ጠቅሰዋል። “የሕዝቡን ስሜት የሚፈነቅል ንግግር” ብለው የጠቀሱላቸው እንዲህ

ይላል:- “ሰላም ይዤላችሁ መጥቻለሁ፤ እኔ የሰላም ምልክት፣ ለሰላም የቆምኩ ነኝ፡፡ አማን ማለት ሰላም ማለት ነው፡፡”
አማን ሚካኤል አንዶም በኤርትራ ጉዳይ ላይ ፌዴሬሽኑ መመለስ እንዳለበት ያምኑ ነበር፡፡ አማን በኤርትራ ጠ/ግዛት

ነዋሪ ዘንድ የተወደዱ ሆኑ፡፡ በእነመንግሥቱ ግን ተጠመዱ፡፡
ከጥቅምቱ የአማን ኤርትራን መጐብኘት ተከትሎ፣ ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ወደ ኤርትራ በመሔድ የተለየ ዘገባ ይዘው

መጡ፡፡ “በአስቸኳይ ጦር ካልተላከ ኤርትራ አለቀላት፣” አሉ፡፡ (ዝ.ከ.53) የአማን “በውይይት ሰላም ይውረድ”፣ ማለት

ቀርቶ የተስፋዬ ወ/ሥላሴ “ጦር ይላክ” በደርጉ ተወሰነ። ፊት ለፊት የታዩ ልዩነቶች አስቀድሞም ነበሩ። ልዩነቱ በዚህ

ላይም ታየ፡፡ አማን ተጠረጠሩ፡፡ ጦሩ በደርግ ላይ እንዲነሳ ቅስቀሳ ጀመሩ ተባሉ፡፡ አማን በኢትዮጵያ አንድነት ላይ

የመጠርጠራቸው ነገር አበሳጫቸው፡፡ ጦር ወደ ሰሜን እንዲላክ ተወስኖ የትኛው ጦር ይሒድ በሚለው ላይም አማን

ሚካኤል አንዶም የተለየ አቋም ያዙ፡፡ ለዚህ ውሳኔ የተደረገውን ስብሰባም ጥለው ወጡ፡፡
ይኽ ኹሉ እየተጨማመረ በሥልጣን ፈላጊዎቹ የደርግ አባላት ዘንድ የአማን ሚካኤል አንዶም ጉዳይ እያበቃቃ መጣ፡፡

እርሳቸውም በግልጽ ይወርፉ ጀመሩ፡፡ “በመሀይማን ጫጫታ አገር አይመራም፣” ይሉ ነበር፡፡
ረቡዕ፣ ኅዳር 7 ቀን 1967 ላይ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጄኔራሉ የማያውቁት ጉብኝት አደረጉ፡፡ የጦር ሠራዊት አባላትን

ሰብስበው ስለ “ኢትዮጵያ ትቅደም” መግለጫ አደረጉ፡፡ ጎፋ ሰፈር በነበረው የታንከኛ ክፍል በመገኘት ይኽን መግለጫ

መስጠታቸው ጄኔራሉን ሥልጣናቸው የይስሙላ ኾኖ እንዲሰማቸው ግድ አለ። “ካልተፈለግሁ፣ ለምልክትነት

አልቀመጥም” አሉ፡፡
በዚኹ ከሥራ ገበታቸው በመቅረት ከቤታቸው ይውሉ ጀመሩ፡፡ በዚህ ርምጃቸው ሥጋት የገባው ደርግ፤ ወደ ጀኔራሉ

መልእክተኞችን መላክ ጀመረ። ይህን ያደረጉት ያኔ ሻለቃ የነበሩት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ ጀኔራል

ግዛው በላይነህና ሻ/ብርሃኑ ባይህን መሪ ያደረገ ልዑክ፣ ቀጥሎ የመረጃ ቢሮ ኃላፊው የነበሩበት ቡድን፣ በኹለቱ ሳይሳካ

ሲቀር ራሳቸው ሻ/መንግሥቱ የሚመሩት ቡድን ቤታቸው ድረስ ሔዶ አነጋገሯቸው፡፡
ከመጨረሻው ቡድን ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ ኃላፊነታቸው ለመመለስ ቻሉ፡፡ በስምምነቱ ውስጥ ኅዳር 7 ቀን 67

መንግሥቱ ያለ ጄኔራሉ ዕውቅና ያደረጉት ጉብኝት በመገናኛ ብዙኃን እንዳይገለጽም ተብሎ ነበር፡፡ የኾነው ግን

በተቃራኒው ነበር፡፡ መንግሥቱ ያደረጉት ጉብኝትና የሰጡት መግለጫ እሑድ ዕለት ኅዳር 11 ቀን 1967 በጦር ኃይሎች

ፕሮግራም ተላለፈ፡፡
ጄኔራሉ በዕለቱ ዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ ለሚያደርጉት ጉብኝት ተነሥተው ሣለ ፣ በሬዲዮ ያ ጉብኝት ሲተላለፍ ሰሙ፡፡

ጉብኝቱን ሰርዘው ተመለሱ፡፡ ከሥራ ገበታቸው በመቅረት እንደገና ቤት መዋል ጀመሩ፡፡ እቤታቸው ኾነው ወደ ተለያዩ

ጦር አዛዦችና መኮንኖች እየደዋወሉ እንዲነሱ ማስተባበሩን ቀጠሉበት፡፡ ይኽ የስልክ ቅስቀሳቸው ግን በደርግ ተጠልፎ

አንድ በአንድ ይያዝ ነበር። በተለይ ከጄኔራል ግዛው በላይነህ ጋር ያደረጉት የስልክ ምልልስ በደርግ ዘንድ ፍርሃትና

ሥጋት ከመፍጠሩም በተጨማሪ የራሳቸው የጄኔራሉን ሕይወትም እንዲቀጭ አደረገ፡፡
“… ግዛው አገራችን በእነዚህ ቂጣቸውን ባልጠረጉ ጨምላቆች ተመርታ ወደ ጥፋት መሔድ የለባትም፡፡ አንተም

ሠራዊትህን አዘጋጅና ይልቅ ተነሣ” ማለታቸው ምስክርነት በተባለው መጽሐፍ ተጠቅሷል (ገጽ 56)
ይህ ቃላቸው ተጠልፎ እንዳለ ለሻለቃ መንግሥቱ ደረሰ፡፡ ሻለቃው ሦስተኛውን ክፍለ ጦር ጠሩ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ

ዙሪያ የነበሩ የፖሊስ ሠራዊትና ልዩ ልዩ ክፍሎችን፣ የንዑስ ደርግ አባላትን ኹሉ ወደ ደርግ ጽ/ቤት በአስቸኳይ ጠሩ፡፡
እንዲህ እያደረጉ ሳለም ጄኔራሉን እንዲይዙአቸው ከክብር ዘብ ሠራዊት 6ኛ ብርጌድ ለተውጣጣ ወታደሮች ትእዛዝ ደርሶ

ነበር፡፡ “እንዴት ብለን በአማን ላይ መሣሪያ እናነሳለን?” አሉና ትዕዛዙን ሳይቀበሉ ቀሩ፡፡ ወደ ሌሎች መለዮ ለባሾች

ትዕዛዙ ዞረ፡፡ እነዚያም እንደዚያው ብለው ሳይቀበሉት ቀሩ። ይህ የጄኔራሉ መወደድና መከበር፣ ይህን ያህል የኾኑት

ጄኔራልም ከደርግ ማፈንገጥ የደርጉን ውድቀት ያመላከተ ኾኖ እስከ መታየት ደረሰ፡፡ ከዚህም የተነሣ በርሳቸው ላይ

የጭካኔ እርምጃ በአፋጣኝና በጠነከረ ኹኔታ እንዲፈጸም እነ መንግሥቱን አሳሰበ፡፡
ፍርሃቱ ግን ጄኔራሉን ብቻ ሳይኾን፣ ታሥረው የነበሩትን የዘውድ አገዛዙ አባላትንና ሌሎችንም ጭምር የሚያኝክበት

ጥርስ እስከማብቀል ደረሰ፡፡ ደርግ መውደቁ ካልቀረ ይጠሏቸው የነበሩትን የንጉሠ ነገሥቱን ባለሥልጣናት ረሚም

አድርጐ እንዲወድቅም ነበር የታሰበው፡፡
መንግሥቱ ኃ/ማርያም ከደብረ ብርሃን አካባቢ ያመጧቸው በዳንኤል የሚመራው ቅልብ ኃይል ወደአማን ተልኮ በተኩስ

ልውውጥ ጄዴኔራሉ ሞቱ፡፡
ይህን የጄኔራሉን ጉዳይ ለመወሰን መንግሥቱ ስብሰባ እየመሩ ሣለ፣ ዳንኤል መጥቶ የጄኔራሉን መገደል ሲነግራቸው፣

“እንግዲህ እምቢ ካሉ በኃይል እጃቸውን እንዲሰጡ ይደረግ” ሲሉ ጮክ ብለው ተሰብሳቢው እንዲሰማው አድርገው

ተናገሩ፡፡
ከዚህ በኋላ በንጉሠ ነገሥቱ ባለሥልጣናት ላይ የግድያ ውሳኔ በድምጽ እንዲወሰን ተደረገ፡፡ “እከሌ” ተብሎ ይጠራል፡፡

“ይገደል” ተብሎ እጅ ይወጣል። ያኔ ማንም “አይገደል” ለማለት አይችልም፡፡ ይገደሉ የተባሉት ከ52ቱ በላይ ነበሩ፡፡

እንደነልዕልት ተናኘወርቅ፣ እንደነንቡረዕድ ኤርምያስ ከበደ፣ እንደነሊቀ ሥልጣናት ኃብተማርያም ያሉ ሌሎችም

ነበሩበት፡፡ የተገደሉት ግን 52ቱ ብቻ ነበሩ፡፡ ቀሪዎቹ 8ቱ የራሱ የደርግና የንዑስ ደርግ አባላት ነበሩ፡፡  

Published in ህብረተሰብ

ኢ/ር ይልቃል ከደጋፊዎቻቸውና ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጋር ይወያያሉ

ሰማያዊ ፓርቲ አፄ ሚኒልክ ያረፉበትን መቶኛ አመት ታህሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር የገለፁ ሲሆን፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ትናንት ወደ ጀርመን በማቅናት ከፓርቲው ደጋፊዎችና ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ይወያያሉ ተባለ፡፡ አፄ ምኒልክ ያረፉበትን መቶኛ ዓመት ለመዘከር በሚዘጋጅ የፓናል ውይይት፣ በምኒልክ ዙሪያ የኢትዮጵያ ምሁራን የጥናት ጽሑፍ እንደሚቀርብ የገለፁት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው በጽሑፎቹ ዙሪያ ሌሎች የአፍሪካ ምሁራንም ይወያያሉ ተብሏል፡፡ እንጦጦ የሚገኘው የምኒልክ ቤተ መንግስትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአፄ ሚኒልክ ፋውንዴሽን የሆነውና ባዕታ ማሪያም አጠገብ የሚገኘው የካህናት ማሰልጠኛና የአረጋዊያን መርጃ እንደሚጐበኙም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ አፄ ምኒልክ በዘመናቸው ምን ዓይነት መሪ እንደነበሩ የሚያሣይ የፎቶ ኤግዚቢሽን በፓርቲው ጽ/ቤት እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡ ፓርቲው፣ የአፄ ምኒልክን ህልፈት መቶኛ አመት ለመዘከር ለምን እንደፈለገ የተጠየቁት አቶ ብርሃኑ፣ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ጋር ከማስተዋወቃቸውም በተጨማሪ በአድዋው ጦርነት ጥቁሮች ነጮችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያሳዩ ቆራጥ መሪ ናቸው ብለዋል፡፡ “በእርሳቸው ዘመን ቴክኖሎጂ እንደ ሰይጣን ይቆጠር ነበር” ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ ከካህናቱና ከቀሳውስቱ ጋር እየተሟገቱ ታላቋን ኢትዮጵያን ቴክኖሎጂ ቀመስ በማድረጋቸው ሊዘከሩ ይገባል ብለዋል አፄ ሚኒልክ በወቅቱ ባቡር፣ ስልክ፣ መኪና፣ ፖስታ፣ ሆቴልና ባንክ በመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ህዝባቸውን ተጠቃሚ አድርገዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ “ዛሬ ስለ ባቡርም ሆነ ስለአጠቃላይ የቴክኖሎጂ ልማት ስናወራ ቅድሚያ መታወስ ያለባቸው አፄ ሚኒሊክ ናቸው” ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል በውጭ አገራት ከሚገኙ ደጋፊዎች በቀረበላቸው ግብዣ ትላንትና ወደ ጀርመን መጓዛቸውን አቶ ብርሃኑ ገልፀዋል፡፡ በሁለት ሳምንታት የጀርመን ቆይታ፣ ኢ/ር ይልቃል በሶስት የአገሪቷ ከተሞች ከደጋፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ የገለፁ ሲሆን፤ ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመወያየት ፕሮግራም ተይዞላቸዋል ብለዋል - አቶ ብርሃኑ፡፡ ኢ/ር ይልቃል ወደ አሜሪካ በማምራት በሰባት ስቴቶች የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታና የፓርቲውን እንቅስቃሴ በማስተዋወቅ ደጋፊዎችን እንደሚያደራጁ አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።

Published in ዜና

የእህል ወፍጮ ሚዛን  የሰረቀው የ4 ዓመት እስር ተበይኖበታል

ከሌሊቱ 9 ሠአት ላይ በካዛንቺስ፣ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ታጥበው የተሰጡ 3 ጅንስ ሱሪዎችን ደራርቦ በመልበስ

ሠርቆ ሲወጣ የተያዘው  ተከሣሽ ሀቢብ አብደላ ኑሪ፤ በፈፀመው ወንጀል በ2 አመት እስራት እንዲቀጣ የፌደራሉ ከፍተኛ

ፍ/ቤት  ሠሞኑን ብያኔ ሰጥቷል፡፡
ተከሣሹ የዛሬ ሦስት ሳምንት ህዳር 2 ሌሊት በልደታ ክፍለ ከተማ፣ ጥይት ፋብሪካ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ

መኖሪያ ግቢ እያንዳንዳቸው 600 ብር የሚያወጡ ሶስት ጅንስ ሱሪዎችን የራሱ አስመስሎ ደራርቦ በመልበስ ሰርቆ

ሲወጣ መያዙ  ተገልጿል፡፡ ፍ/ቤቱም ሠሞኑን “የተከሣሹ ድርጊት ሌሎችንም ያስተምራል” በሚል በ2 አመት እስራት

እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል በልደታ ክ/ከተማ የግለሠቦችን መኖሪያ ግቢ ሠብሮ በመግባት 5ሺህ ብር የሚገመት የእህል ወፍጮ ሚዛን

የሠረቀውና በሊስትሮነት የሚተዳደረው ወጣት ሠለሞን ፀጋዬ ላይ የ4 አመት እስራት በይኖበታል፡፡

Published in ዜና

ንጉሥ አፄ ኃይለሥላሴ ለበጎ አድራጐት እንዲውል ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ባሠሩት ሕንፃ ውስጥ የሚኖሩ ተከራዮች፣ ዓመት ሳይሞላ ሁለት ጊዜ 120 እና 600 ፐርሰንት የሚደርስ የቤት የኪራይ ጭማሪ ተደረገብን ሲሉ አማረሩ፡፡ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ሴቶች ፈንድ፣ ቀጥሎም የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በተባለው ሕንፃ የሚኖሩ ተከራዮች፤ መኝታ ክፍል የሌለው 43 ካ.ሜ ስቱዲዮ 2005 ብር ይከፍሉ የነበረው 600 ፐርሰንት ያህል ጭማሪ ተደርጐባቸው 9.030 ብር፣ 90ካ.ሜ የሆነው ባለ ሁለት መኝታ ክፍል 3.495 ብር የነበረው 20.370 ብር እንዲከፍሉ በመጠየቃቸው፣ ቅሬታና በደላቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በደብዳቤ ገልፀው ከመበተን እንዲያድኗቸው ጠይቀዋል፡፡ ነዋሪዎቹ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ፣ ባለፈው መጋቢት ወር ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ የወቅቱን ሁኔታ ያላገናዘበ የ120 ፐርሰንት ጭማሪ ተደርጐብን ምንም አማራጭ ስለሌለን፣ ፍትሐዊ ያልሆነውን የኪራይ ጭማሪ ተሸክመን ሳለ፣ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በያዝነው ወር፣ እስከ 600 ፐርሰንት የሚደርስ የኪራይ ጭማሪ ተደረገብን በማለት ማመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአሁን በፊት የተደረገውን ኢ-ፍትሐዊ የቤት ኪራይ ጭማሪ፣ ልጆቻችንን ካስገባንበት ት/ቤቶችና ለመ/ቤቶቻችን ባለው ቅርበት ሳንወድ ብንቀበለውም፣ ድርጅቱ የፈፀመብን በደል አልበቃ ብሎትና የቆመለትን ማኅበራዊ ኃላፊነት በመዘንጋት፣ በቤት ኪራይ ጭማሪው ተስማምተን እንድንኖር፣ ካልሆነም ኅዳር 30 ቀን 2006 ዓ.ም ቤቱን እንድንለቅ ውሳኔ ማስተላለፉ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ መንግሥት በውጭ አገራት በደልና እንግልት የተፈፀመባቸውን ዜጐች ወደ አገራቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረትና ርብርቦሽ እያደረገ፤ የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት ለማረጋገጥና በዘርፉ የሚታየውን የቤት ችግር ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እየተጋ ባለበት ወቅት፣ ዜጐችን ያለ አግባብ ማፈናቀል፣ በሥርዓቱ ላይ ጥላቻ እንዲያድርብን ከማድረጉም በላይ፣ የተያያዝነውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስለሚቃረን በእንጭጩ መገታት እንዳለበት እናምናለን ብለዋል፡፡ በሕንፃው ውስጥ ከ10 እስከ 36 ዓመታት መኖራቸውንና በራሳቸው የተመዘገበ ቤት እንደሌላቸው የጠቀሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከ40 እስከ 80 ዕድሜ ውስጥ ያሉ ስለሆነና ቤት ተሯሩጠው ለማግኘት አቅም ስለሌላቸው፣ ከ40 በላይ ሰዎች የሚያስተዳድሩት አባወራዎች ሜዳ ላይ ከመበተናቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰብአዊ ውሳኔ እንዲሰጧቸው ተማፅነዋል፡፡ ተከራዮቹ 120 ፐርሰንት በተጨመረባቸው ጊዜ መኝታ ክፍል ለሌለው 43 ካ.ሜ ስቱዲዮ፣ 2005 ብር ይከፍሉ የነበረው በአዲሱ ጭማሪ 9,030 ብር፣ ባለ ሁለት መኝታ 90 ካ.ሜ ክፍል፣ ባለፈው ዓመት ጭማሪ 3,495 ብር፣ በአዲሱ ደግሞ 20,370 ብር እንዲከፍሉ እንደተወሰነባቸው አስረድተዋል፡፡

Published in ዜና

ሞባይሌን ወስዶብኛል፤ ይመልስልኝ በሚል ሠበብ፣ የጁስ ቤት ሠራተኛ የሆነውን ግለሠብ በገጀራ በመምታት በጥርሡ
እና በአፍንጫው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሠው ኢዮብ አድነው የተባለ ተከሣሽ፤ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ20 አመት ፅኑ

እስራት ተፈርዶበታል፡፡
በሌለበት የተከሠሠው አቶ ኢዮብ፤ የግል ተበዳይን ለመግደል አስቦ መስከረም 21 ቀን 2005 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 1

ሠአት ላይ በልደታ ክ/ከተማ፣ አብነት አደባባይ አካባቢ ወደሚገኝ ስሙ ያልተገለፀ ጁስ ቤት በማምራት፣ ወንጀሉን

መፈፀሙን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አቃቤ ህግ አቅርቧል፡፡
ሠሞኑን የዋለው 10ኛ ወንጀል ችሎት፤ ተከሣሹ በሌለበት የአቃቤ ህግን 3 የሠው ማስረጃ መሠረት በማድረግ፣ “ክሡን

በሚገባ አልተከላከለም” በማለት ተከሣሹ በ20 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣና እስራቱን ሲጨርስ ለ3 አመታት

ከማንኛውም ህዝባዊ መብቱ እንዲታገድ በይኗል፡፡    

Published in ዜና
Saturday, 30 November 2013 10:35

ኢትዮጵያ በሴካፋ ላይ…

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አስቀድሞ ከ2004 እሰከ 2006 እኤአ ብሄራዊ ቡድኑን በዋና

አሰልጣኝነት ሲመሩ በ5 ዓመት ውስጥ 3 የሴካፋን ዋንጫዎችን  ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለማግኘት በቅተዋል፡፡

በ2005 እ.ኤ.አ በሩዋንዳ ላይ እንዲሁም በ2004 እ.ኤ.አ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎችን በዋና

አሰልጣኝነት ያሸነፉት ሰውነት በ2001 እ.ኤ.አ በረዳት አሰልጣኝነት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሴካፋን ዋንጫ ሩዋንዳ ላይ

እንዳገኙ ይታወቃል፡


በኬንያ አስተናጋጅነት ከተጀመረ አራተኛ ቀኑን በያዘው 37ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው የእግር ኳስ ሻምፒዮና በተስፋ

ቡድኗ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ ከምድቡ ለማለፍ ዛሬ ከዛንዚባር ጋር በምታደርገው ወሳኝ ጨዋታ ማሸነፍ

ይጠበቅበታል፡፡ የምድብ 1 የመጀመርያ ግጥሚያዎች ባለፈው ረቡዕ  ተደርገው በከፍተኛ ጉጉት የተጠበቀው የአዘጋጇ

ኬንያ እና ኢትዮጵያ ጨዋታ ያለንምንም ግብ 0ለ0 ሲጠናቀቅ፤ በሌላ የምድቡ ጨዋታ ደግሞ ዛንዚባር 2ለ0 ደቡብ

ሱዳንን አሸንፋለች፡፡ በሻምፒዮናው የምድብ 1 ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ ኢትዮጵያ ከዛንዚባር ፤ ኬንያ ደግሞ

ከደቡብ ሱዳን ጋር ይጫወታሉ፡፡ ኢትዮጵያን የወከለው ተስፋ ቡድን ከምድብ 1 የማለፍ እድሉን ለመወሰን ከዛንዚባር

ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ማሸነፍ ብቸኛው አማራጩ ሲሆን ካልቀናው ሰኞ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያደርገው የምድቡ

የመጨረሻ ጨዋታ መርሃግብሩን ለመጨረስ የሚካሂደው ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2005 እኤአ ላይ

ለአራተኛ ጊዜ የዞኑ ሻምፒዮን ለመሆን ከበቃ ወዲህ ያን ያህል ጠንካራ ውጤት ሊያስመዘግብ አዳግቶታል፡፡ በዘንድሮው

የሴካፋ ውድድር ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ፤ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ጥሎ ማለፍ

ምእራፍ በመድረስ እና የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ተሳትፎውን ያረጋገጠውን ዋና ቡድኗን ባለማሰለፏ ከዋንጫው

ግምት ውጭ ያደረጋት ሲሆን የተስፋው ቡድን ከሩብ ፍፃሜ ለማለፍ እንኳን ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው እየተገለፀ

ነው፡፡ ባለፈው ረቡዕ የተስፋ ቡድኑ ከኬንያ ጋር 0ለ0 አቻ ከተለያየ በኋላ አስተያየታቸውን ለሱፕር ስፖርት የሰጡት

አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሴካፋው ተሳትፎ ብሄራዊ ቡድናቸው ለቻን ውድድር ጠቃሚ ልምድ ሊያገኝበት አስቦ

የሚወዳደረው መሆኑን ገልፀው፤ ለውድድሩ ከአራት ቀናት ያነሰ ዝግጅት ማድረጋቸው ለምድቡ የመጀመርያ ጨዋታ በቂ

ሁኔታ አልነበረምም ብለዋል፡፡ ፡ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር በናያዮ ስታድዬም ያደረገችውን ግጥሚያ በርካታ ተመልካች

የታደመው ሲሆን በተለይ በተከላካይ መስመር ተሰልፈው የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሳላዲን በርጌቾ እና የኢትዮጵያ

ቡናው ቶክ ጀምስ ምርጥ ብቃት ማሳየታቸውን ሱፕር ስፖርት ዘግቦታል፡፡ ከምድብ 1 የመጀመርያ ጨዋታዎች በኋላ ወደ

ቀጣዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር እድል አላቸው ከተባሉት ኬንያና ኢትዮጵያ ይልቅ ዛንዚባር ሁኔታዎች ተመቻችተውላታል፡፡  

ቀድሞ የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች በነበሩት ሳሉ ሙናሽሮ የሚሰለጥነው የዛንዚባር ብሄራዊ ቡድን በፊፋ እውቅና

ያላገኘ ሲሆን የተመዘገበው በታንዛኒያ ቡድን አካል ሆኖ ነው፡፡ ዛንዚባር በሴካፋ የረጅም ጊዜ ተሳትፎ ታሪኳ በ1995

እኤአ ላይ ብቸኛውን የዋንጫ ድል አስመዝግባለች፡፡ የ37ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና  አዘጋጅ

የሆነችው ኬንያ በውድድሩ ሻምፒዮን ከሆነች 11 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኬንያ በሴካፋ ሻምፒዮና ለአምስት ጊዜ

ዋንጫውን በማንሳትና 6 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ በማግኘት በምንጊዜም የውጤት ደረጃ ሁለተኛ ስትሆን በፊፋ የእግር ኳስ

ደረጃዋ 118ኛ ነው፡፡ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ በሴካፋ ዞን ውድድር ስትሳተፍ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜዋ የሚሆነው ደቡብ

ሱዳን የባንግላዴሽ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በነበሩት ዞራን ዶርዴቪች ትመራለች፡፡ ደቡብ ሱዳን በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ

የመጨረሻውን 205ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ከተጀመረ ከ87 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩ የዓለማችን

አንጋፋው የእግር ኳስ ውድድር ያደርገዋል፡፡ የእግር ኳስ ሻምፒዮናው በ1926 እኤአ ላይ ተጀምሮ 1983 እስከ 1966

እኤአ ድረስ በዊልያም ጎሴጅ የሳሙና ፋብሪካ ስፖንሰርነት ሲካሄድ ጎሴጅ ካፕ ተብሎ ለ37 ጊዜያት የተከናወነ ነበር፡፡

ከ1967 እስከ 1971 እኤአ ለአምስት ጊዜያት የዞኑ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ፓልሜሬስ ካፕ ተብሎም ተካሂዷል፡፡ በጎሴጅ

እና ፓልሜሬስ ካፕ ተሳታፊ የነበሩት አገራት ኬንያ፤ ኡጋንዳ፤ ታንጋኒካ እና ዛንዚባር ናቸው፡፡
በሴካፋ ምክርቤት ስር የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ‹‹ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ተብሎ ››መካሄድ

የተጀመረው በ1973 እኤአ  ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችው ደግሞ በ1983 እኤአ ላይ በኬንያ

ሲካሄድ ነበር፡፡ በወቅቱ በምድብ 1 ከኬንያ፤ ከኡጋንዳ፤ ከሱዳንና ከታንዛኒያ ጋር ተደለደለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን

በመጀመርያ ጨዋታ ከታንዛኒያ አንድ እኩል አቻ ከተለያየ በኋላ፤ በኬንያ 2ለ0፤ በሱዳን 2ለ0 እንዲሁም በኡጋንዳ 2ለ1

ተሸንፎ በ1 ነጥብ የምድቡን የመጨረሻ ደረጃ በመያዝ ተሰናብቷል፡፡ ከዚሁ የመጀመርያ ተሳትፎ በኋላ 3 የምስራቅ እና

መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ውድድሮች ያመለጣት ኢትዮጵያ በ1987 እኤአ ላይ ውድድሩን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ

የማስተናገድ እድል አገኘች፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተደረገው በዚሁ 15ኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር

ኳስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በምድብ 1 የተደለደለችው ከዛንዚባር፤ ከኬንያ እና ከታንዛኒያ ጋር ነበር፡፡ በመጀመርያዎቹ

የምድቡ ሁለት ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከታንዚያ እና ከዛንዚባር ጋር ያለምንም ግብ 0ለ0 በሆነ ተመሳሳይ

ውጤት ነበር የተለያየው፡፡ በመጨረሻ ጨዋታ ኬንያን 2ለ1 ካሸነፈ በኋላ ግን በ4 ነጥብ በምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ

በመጨረስ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ገባ፡፡ በግማሽ ፍፃሜው የተገናኘው ከኡጋንዳ ጋር ሲሆን 3ለ0 አሸነፈ፡፡ ኢትዮጵያ

ለመጀመርያ ጊዜ ባስተናገደችው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ላይ ብሄራዊ ቡድኑ ለመጀመርያው የዋንጫ

ጨዋታው ሲቀርብ የተገናኘው ከደቡብ አፍሪካ በተጋባዥነት ከተሳተፈችው ዚምባቡዌ ጋር ነበር፡፡ በመደበኛው የጨዋታ

ክፍለ ጊዜ 1 እኩል አቻ ሆኑ፡፡ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡ የመለያ ምቶች ኢትዮጵያ 4ለ3 ዚምባቡዌን በማሸነፍ

የመጀመርያውን  የሻምፒዮናነት ክብር ለማሳካት በቃች፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቀጣይ ሻምፒዮናነቱን ለማስጠበቅ የተሳተፈበት የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና

በ1988 እኤአ ላይ በማላዊ የተካሄደው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 2 ከዛምቢያ፤ ከዚምባቡዌ እና ከኡጋንዳ ጋር ነበረች፡፡

ከዛምቢያ ጋር 0ለ0 የተለያየው የኢትዮጵያ ቡድን በሁለተኛ ጨዋታው ኡጋንዳን 2ለ1 ቢያሸንፍም በመጨረሻ በዚምባቡዌ

2ለ1 በመረታተቱ በ3 ነጥብ የምድቡን 3ኛ ደረጃ ይዞ በጊዜ ሻምፒዮናነቱን ሳያስጠበቅ ተሰናብቷል፡፡
ኢትዮጵያ በ1989 እኤአ በኬንያ፤ በ1990 እኤአ በዛንዚባር እና በ1991 እኤአ ላይ በኡጋንዳ በተካሄዱት ሶስት የምስራቅ

እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮናዎች ሳትሳተፍ ቀረች፡፡ በ1992 እኤአ ላይ ውድድሩ በታንዚያ ሲካሄድ ኢትዮጵያ

ተመልሳ ወደውድድሩ በመቀላቀል ከማላዊ፤ ከዛምቢያ፤ ከታንዛኒያ እና ከዛንዚባር ጋር በምድብ 2 ተመደበች፡፡ ዛንዚባርን

3ለ0 በማሸነፍ ጥሩ አጀማመር አሳይቶ የነበረው ቡድኑ በዛምቢያ 3ለ2፤ በታንዛኒያ 2ለ1 እንዲሁም በማላዊ 2ለ1

ተደራራቢ ሽንፈት ደርሶበት በ2 ነጥብ ከምድብ ሳያልፍ ቀረ፡፡ በቀጣይ በ1994 እኤአ ላይ ውድድሩን ኬንያ ስታስተናግድ

ኢትዮጵያ አልነበረችም፡፡ በ1995 እኤአ ላይ ውድድሩ በኡጋንዳ ሲዘጋጅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ገብቶ በምድብ 2

ከኡጋንዳ ቢ፤ ከታንዛኒያ እና ከሶማሊያ ተገናኘ፡፡ ከታንዛኒያ ጋር 2 እኩል አቻ በመለያየት የምድብ ፉክክሩን የጀመረው

ቡድኑ የኡጋንዳ ቢ ቡድንን 1ለ0 ከዚያም ሶማሊያን 3ለ0 አሸንፎ በ7 ነጥብ የምድቡ መሪ ሆኖ አለፈ፡፡ በግማሽ ፍፃሜ

የተገናኘው  ከዛንቢያ ጋር ሲሆን በመደበኛው እና በተጨማሪዎቹ የጨዋታ ክፍለ ጊዜዎች 1 እኩል ከተለያየ በኋላ

አሸናፊውን ለመለየት በተደረጉ የመለያ ምቶች ተሸነፈ፡፡ በመቀጠል ለደረጃ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከኬንያ ጋር

ተጫውቶ 2ለ1 በማሸነፍ በሶስተኛ ደረጃ ተሳትፎውን ደምድሞታል፡፡ በ1996 እኤአ  ሱዳን ላይ እንደሚካሄድ ተወስኖ

የነበረውና በ1997 እኤአ አዘጋጅ አገር ባለመመረጡ ሁለት የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮናዎች

አልተካሄዱም፡፡  በ1998 እኤአ ላይ በሩዋንዳ ውድድሩ ሊካሄድ ታቅዶ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በሴካፋ

ምክርቤት ላይ እግድ በመጣሉ እና ከ1998ቱ የዓለም ዋንጫ በፊት በፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመደረጉ ጋር በተያያዘ

ሻምፒዮናው በድጋሚ ሳይካሄድ ተሰርዟል፡፡ በዚህ ውድድር ለመሳተፍ ፍላጎት የነበራት ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከሩዋንዳ፤

ከኡጋንዳና ከብሩንዲ ጋር ተደልድላ ነበር፡፡ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ለ4 ዓመታት ሳይካሄድ

ውጣውረድ ከቆየ በኋላ በ1999 እኤአ ላይ የተዘጋጀው በሩዋንዳ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 3 ከሱዳንና ዛንዚባር ጋር

ተመደበች፡፡  ዛንዚባርን 2ለ0 ያሸነፈው ቡድን ከሱዳን ጋር ለ0 አቻ ተለያይቶ በ4 ነጥብ የምድቡ መሪ ሆኖ አለፈ፡፡

በሩብ ፍፃሜ ምእራፍ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተገናኘው ከሩዋንዳ ቢ ቡድን ጋር ቢሆንም 1ለ0 ተሸንፎ ከውድድሩ

ውጭ ሆኗል፡፡
በ2000 እኤአ ላይ አዘጋጇ ኡጋንዳ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከኡጋንዳ፤ ከብሩንዲ፤ ከጅቡቲ እና ከሶማሊያ ጋር

ተደለደለች፡፡ በመጀመርያ ጨዋታ ከኡጋንዳ ጋር 2ለ2 አቻ ስትለያይ ለኢትዮጵያ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ስንታየሁ ጌታቸው

እና ሁሴን ሰማን ነበሩ፡፡ ሶማሊያን 2ለ1 ስታሸንፍ ደግሞ ግቦቹን ስንታየሁ ጌታቸው እና ሁሴን ሰማን አስቆጥረዋል፡፡

በምድቡ 3ኛ ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጅቡቲን 4ለ2 ያሸነፈ ሲሆን ጎሎቹን ሁለቱን እስማኤል አቡበከር፤

እንዲሁም ስንታየሁ ጌታቸውና እና ጌቱ ተሾመ የተቀሩትን አስመዝግበዋል፡፡ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ቡድኑ ብሩንዲን

1ለ0 ሲያሸንፍ ጎሏን ያስመዘገበው እስማኤል አቡበከር ነበር፡፡ በምድብ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ

ብቃቱን ያስመዘገበበት አቋም ለዋንጫው ግምት ያሳደረ ነበር፡፡ ምድቡን በ10 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ በሁለተኛ ደረጃ

የጨረሰው ቡድኑ በግማሽ ፍፃሜ የተገናኘው ከኡጋንዳ ጋር ሲሆን ሳይጠበቅ 1ለ0 ተሸንፎ ለደረጃ መጫወት ግድ

ሆነበት፡፡ ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተገናኘው ከሩዋንዳ ሲሆን 1ለ1 አቻ ተያይዞ ቢቆይም

በመለያ ምቶች 4ለ2 ተሸንፎ በ4ኛ ደረጃ ጨርሷል፡፡
በ2001 እኤአ ላይ ሱዳን አዘጋጃለሁ ብላ የሰረዘችውን ሻምፒዮና በምትክነት ያስተናገደችው ሩዋንዳ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ

በምድብ 3 ከሩዋንዳ ቢ ቡድንና ዛንዚባር ጋር ተመደበች፡፡ ዛንዚባርን በመጀመርያ ጨዋታ 5ለ0 ስታሸንፍ ይልማ፤

አፈወርቅ፤ ዮርዳኖስ ፤ ፈቃዱ እና ባዩ ሙሉ ጎሎቹን ከመረብ አዋህደዋል፡፡ በመቀጠል ከሩዋንዳ ቢ ቡድን ጋር 1ለ1 አቻ

ስትለያይ ጎሎን ያገባው ባዩ ሙሉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በ4 ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና አለፈች፡፡ በሩብ ፍፃሜ ከብሩንዲ ጋር

የተገናኘው ቡድኑ በጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2ለ2 አቻ ተለያየየ፡፡ ጎሎቹ የዮርዳኖስ አባይና ባዩ ሙሉ ናቸው፡፡ አሸናፊውን

ለማወቅ መለያ ምቶች ተሰጥተው ኢትዮጵያ 5ለ4 ብሩንዲን አሸንፋ ግማሽ ፍፃሜ ገባች፡፡ በግማሽ ፍፃሜው ሩዋንዳን

ስታሸንፍ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል ያስመዘገበው ባዩ ሙሉ ነበር፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለዋንጫ

ጨዋታ ከኡጋንዳ ጋር ተገናኘ፡፡ ማሞዓለም ሻንቆ እና ዮርዳኖስ አባይ ባስቆጠሯቸው  ጎሎች 2ለ1 በማሸነፍ የኢትዮጵያ

ብሄራዊ ቡድን ለሁለተኛ ጊዜ የሴካፋ ሻምፒዮን ለመሆን በቃ፡፡ ይህ የዋንጫ ድል ከአገር ውጭ የተገኘ በመሆኑ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ  አበይት ስኬት ሆኖ ለመጠቀስ የበቃ ነበር፡፡ በ2002 እኤአ  የምስራቅ እና መካከለኛው

አፍሪካ ሻምፒዮናን ያስተናገደችው ታንዛኒያ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 2 ከኡጋንዳ፤ ሩዋንዳ እና ዛንዚባር ጋር

ተደለደለች፡፡ ከዛንዚባር ጋር 0ለ0 የተለያየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኡጋንዳ 3ለ0 ሲሸነፍ አንተነህ አላምረው

በራሱ ላይ አግብቶ ነበር፡፡ በ3ኛው የምድቡ ጨዋታ ሻምፒዮናነቱን ያስጠብቃል ተብሎ የነበረው ቡድኑ ባልተገመተ

ሁኔታ በሶማሊያ 1ለ0 ተሸነፈ፡፡ ከዚያም በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ በድጋሚ በሩዋንዳ 1ለ0 ተረትቶ ሻምፒዮናነቱን

ሊያስጠብቅ ሳይችል በ1 ነጥብ የምድቡ መጨረሻ ደረጃ ይዞ ውድድሩ ተሰናብቷል፡፡ በ2003 እኤአ ላይ  የምስራቅ እና

መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮናን ሱዳን ስታዘጋጅ ኢትዮጵያ በምድብ 2 ከኬንያ፤ ኡጋንዳ እና ኤርትራ ጋር ተደልድላ

የነበረ ቢሆንም ሳትሳተፍ ቀረች፡፡
በ2004 እኤአ ላይ ክቡር ሼህ መሃመድ አላሙዲ የሴካፋ ውድድርን ስፖንሰር በማድረጋቸው የእግር ኳስ ሻምፒዮናው

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ሊካሄድ በቃ፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተደረገው በዚሁ ውድድር

ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከብሩንዲ፤ ከሩዋንዳ፤ ከዛንዚባር እና ታንዛኒያ ጋር ነበር የተመደበችው፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ

ሰብስቤ ሸገሬ እና ፍቅሩ ተፈራ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ብሩንዲን 2ለ1 ያሸነፈው ቡድኑ በመቀጠል ከሩዋንዳ ጋር 0ለ0 አቻ

ተለያየ፡፡ በሶስተኛው የምድቡ ጨዋታ ታንዛኒያን 2ለ0 ድል ማድረግ የተቻለው በአንተነህ አላምረው እና በታፈሰ ተስፋዬ

ጎሎች ነበር፡፡ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡድን ዛንዚባርን 3ለ0 ሲያሸንፍ ጎሎቹን ፍቅሩ ተፈራ፤

አሸናፊ ግርማ እና ሃይደር መንሱር አግብተዋል፡፡ በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ቡድን ምድቡን በ10 ነጥብ በመምራት ግማሽ

ፍፃሜ ገባ፡፡ በግማሽ ፍፃሜው  ከኬንያ ጋር የተገናኘው ቡድኑ አንተነህ አላምረው እና ታፈሰ ተስፋዬ ባስቆጠሯቸው

ጎሎች ሁለት እኩል አቻ ከተለያየ በኋላ በመለያ ምት አሸናፊው ሲለይ 5ለ4 ረትቶ ለሶስተኛ ጊዜ በሴካፋ ሻምፒዮና

የዋንጫ ጨዋታ ላይ ቀረበ፡፡ በዋንጫ ጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ብሩንዲን በአንዷለም ንጉሴ፤ በታፈሰ ተስፋዬ

እና በአንተነህ አላምረው ጎሎች 3ለ0 በማሸነፍ በታሪክ ለሶስተኛ ጊዜ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና

ዋንጫን ተጎናፀፈ፡፡
በ2005 እኤአ ላይ የውድድሩ አዘጋጅ የሆነችው ሩዋንዳ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ሻምፒዮንነቷን ለማስጠበቅ ተስፋ አድርጋ

በምድብ 2 ከኡጋንዳ፤ ከሱዳን፤ ከሶማሊያ እና ከጅቡቲ ጋር ተመደበች፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ ከኡጋንዳ ጋር 0ለ0

ከተለያየች በኋላ በሁለተኛው ግጥሚያ ሱዳንን 3ለ1 የረታችው በሰብስቤ ሸገሬ ሃትሪክ ነበር፡፡ በቀጣይ የኢትዮጵያ

ብሄራዊ ቡድን ጅቡቲን 6ለ0 እንዲሁም ሶማሊያን 3ለ1 በማሸነፍ በ10 ነጥብ የምድቡን ሁለተኛ ደረጃ ይዞ አለፈ፡፡

በግማሽ ፍፃሜ ቡድኑ ዛንዚባርን 4ለ0 ሲያሸንፍ ፍቅሩ ተፈራ ሃትሪክ የሰራ ሲሆን አንደኛዋን ጎል ደግሞ አሸናፊ ግርማ

አስመዝግቧታል፡፡ በዋንጫ ጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተገናኘው ከሩዋንዳ ጋር ሲሆን በጨዋታው

የማሸነፊያዋን ብቸኛ ጎል ያገባው በቀይ ካርድ የወጣው አንዱዓለም ንጉሴ ነበር፡፡ በዚህም ውጤት የኢትዮጵያ ብሄራዊ

ቡድን በተከታታይ ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ሆኖ ሻምፒዮናነቱን ከማስጠበቅ ባሻገር በተሳትፎ ታሪኩ አራተኛውን ዋንጫ

ለማግኘት ችሏል፡፡
በ2006 እኤአ ላይ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ውድድርን ለአራተኛ ጊዜ የማስተናገድ እድሉን ያገኘችው

የአራት ግዜ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ በምድብ 1 ከታንዛኒያ፤ ከማላዊ እና ከጅቡቲ ጋር ተመድባ ነበር፡፡

በመጀመርያው ጨዋታ በታንዛኒያ 2ለ1 ስትሸነፍ የማፅናኛዋን ጎል ያስመዘገበው ቢኒያም ታፈሰ ነበር፡፡ በመቀጠል ጅቡቲን

በዳዊት መብራቱ፤ ታፈሰ ተስፋዬ፤ ባህይሉ ደመቀና ብዙነህ ወርቁ ጎሎች 4ለ0 የረታው የኢትዮጵያ ቡድን ማላዊን

በዳዊት መብራቱ ጎል 1ለ0 በማሸነፍ ለሩብ ፍፃሜው የበቃው በ6 ነጥብ የምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ነበር፡፡ በሩብ ፍፃሜው

በሜዳው እና በደጋፊው የተጫወተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዛምቢያ 1ለ0 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆነ፡፡ በአዲስ

አበባ ተደርጎ የነበረውን የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ዋንጫንዛምቢያ ሱዳንን በመለያ ምቶች 11ለ 10  

በማሸነፍ ወስዳለች፡፡ በ2007 እኤአ ላይ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና  በታንዛኒያ አዘጋጅነት ሲካሄድ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 3 ከዛንዚባር እና ሱዳን ጋር ተደልድሎ ነበር፡፡ በምድቡ የመጀመርያ ጨዋታ

በዛንዚባር 3ለ1 የተሸነፈው ቡድኑ ከሱዳን ጋር ያለምንም ግብ አቻ ከተለያየ በኋላ በ1 ነጥብ መጨረሻ ደረጃ ይዞ

ከውድድሩ የምድብ ምእራፍ ተሰናብቷል፡፡ ሻምፒዮናው በ2008 እኤአ መካሄድ ሲቀጥል አጋጇ ኡጋንዳ የነበረች ሲሆን

ኢትዮጵያ አልተሳተፈችበትም ነበር፡፡ በ2009 እኤአ ላይ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና የተካሄደው ኬንያ

ላይ ነው፡፡ በዚሁ ውድድር ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከዛምቢያ፤ ከኬንያ እና ከጅቡቲ ጋር ተደልድላለች፡፡ በመጀመርያ

ጨዋታ ጅቡቲን 5ለ0 ላሸነፈው የኢትዮጵያ ቡድን ጎሎቹን ያስቆጠሩት ሁለቱን ኡመድ ኡክሪ እንዲሁም ሌሎቹን አየነው

አክሊሉ፤ አዳነ ግርማና ታፈሰ ተስፋዬ ናቸው፡፡ በቀጣይ በተደረጉት የምድብ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ቡድን በዛምቢያ

1ለ0 እንዲሁም በኬንያ 2ለ0 በመሸነፉ ከውድድሩ በጊዜ መሰናበት ግድ ሆኖበታል፡፡
በ2010 እና በ2011 እኤአ ላይ ሻምፒዮናው የተስተናገደው የሴካፋ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሊዮዳር ቴንጋ አገር በሆነችው

ታንዛኒያ ውስጥ ነበር፡፡  በ2010 እኤአ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 3 ከኡጋንዳ ፤ ከኬንያ እና ከማላዊ

ተደልድሎ ነበር፡፡  በመጀመርያው ጨዋታ ቡድኑ በኡጋንዳ 2ለ1 ቢሸነፍም በቀጣይ ኬንያን 2ለ1 በመርታት እንዲሁም

ከማላዊ 1ለ1 አቻ በመለያየት ከምድቡ ማለፉን አረጋገጠ፡፡ በሩብ ፍፃሜ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛምቢያን 2ለ1 አሸንፎ

በግማሽ ፍፃሜ ከአይቬሪኮስት በመገናኘት 1ለ0 ተሸንፎ ውድድሩን በ4ኛ ደረጃ አገባድዷል፡፡በ2011 እኤአ ላይ ሴካፋው

በታንዛኒያ በድጋሚ ሲደረግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  የገባው ለዋንጫው ግምት አግኝቶ ነበር ፡፡ በወቅቱ በምድብ 3

ከማላዊ፤ ከሱዳንና ከኬንያ ጋር ተደልድሏል፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ ከሱዳን ጋር አቻ ሲለያይ ጎል ያገባው ጌታነህ ከበደ

ነበር፡፡ ከዚያም በኬንያ 2ለ0 ተሸነፈ እና በመጨረሻው ጨዋታ አሁንም በጌታነህ ከበደ ጎል 1 እኩል  ከማሊ ጋር አቻ

ወጥቶ ከምድብ ማጣርያው ውድድሩን ተሰናብቶታል፡፡ በ2012 እኤአ ላይ ውድድሩ  በኡጋንዳ ነበር የተዘጋጀው፡፡

ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከዩጋንዳ ከደቡብ ሱዳንና ከኬንያ ጋር ነበረች፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ ደቡብ ሱዳንን 1ለ0

ያሸነፈው ቡድኑ በዩጋንዳ 1ለ0 እንዲሁም በኬንያ 3ለ1 ቢሸነፍም በአወዛጋቢ ሁኔታ በምድብ ምርጥ ሶስተኛነት ወደ

ቀጣይ ምዕራፍ ሊሸጋገር በቅቷል፡፡ ይሁንና ሩብ ፍፃሜ ላይ 2ለ0 በኡጋንዳ ተሸንፎ ተሳትፎውን ጨርሷል፡፡ በወቅቱ  

በሴካፋው የተሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን በወቅቱ ለአፍሪካ ዋንጫ ላለፈው ዋና ብሄራዊ ቡድን ‹‹ሻዶው ቲም›› ተብሎ

የብሄራዊ ቡድኑ ረዳት አሰልጣኝ በነበሩት በስዩም ከበደ የሚመራ ነበር፡፡

መልስ አልባ ጥያቄ መልስ እንዳለው ያውቃል
ምልእቲ ኪሮስ
ምስልሽን ለመሳል መች አልወጠርኩ ሸራ
ዓይንሽን ለማየት መች አጣኝ መከራ
የዓይንሽን ብሌን ቅንድብሽን አስታውሶ
የስዕልን ብሩሽ በፍቅር ቃል ለውሶ፤ ቀለም ማንጠባጠብ
በመውደድሽ ምትሀት በፍቅርሽ መተብተብ
ከዚያም ቀለም ማፍሰስ …….
ማፍሰስ … ማፍሰስ … ማፍሰስ …
በማፍቀር መ ኮ ፈ ስ!!
ከጠጉሮችሽ መሀል ገብቶ መንፈላሰስ
ድንገት ያምረኝና … ድንገት ያምረኝና
ከበድን ሸራዬ ጠጉር እስልና
ዕልመት እስልና
ከብርሀን ግንባርሽ፣ ከዕድሜ ቀጣይ ዓይንሽ፣ ድንገት እደርስና
ከጠጉርሽ ጥቁር ፅልማት ቀላቅዬ ብሌንሽን ቀባለሁ … ደሞ ፀልያለሁ
ጥቁርሽን ‘ሚያሳዬኝ ዓይኔን አጥፋ እላለሁ
ብሌንሽ ተቀባ ዳር ዳሩ ተኳለ
የእግዚሀር መልኩ ጠፋ
ከኔ ምስልሽ አለ ፊቴ ካለው ፊትሽ
ምስልሽ ሸራዬ ላይ ቡሩሼ ላይ ወዝሽ
ድምፅሽ ላይ ትዝታ … ድምጼ ላይ ስቅታ
ስቅታዬ ደስታሽ ሳጌ ደማቅ ሳቅሽ
ታዲያ እንዲ አይደል ስዕል?
ካንቺ እየተያዩ ቀለም መቀላቀል
ሰማያዊ ህብር ከቀዩ መቀየጥ
ከጥቁሩ ነክሮ ነጩ ላይ መገልበጥ
ከስዕል ሸራ ላይ ዓይንን ተክሎ ማደር
ኋላም መጮህ ማበድ በቀለማት መስከር
ማይታወቅ ቀለም እስኪመጣ ድረስ
አንዱን ካንዱ መድፋት እላዩ ላይ ማፍሰስ
በእጅ እያፈሱ ወደ ሰማይ መርጨት
ምስልሽን ሽቶ ከአምላክ መጋጨት
ጠያቂን መጠየቅ … ጥያቄን … ማስጨነቅ
የቆዳዋን አይነት ቀለም ደባልቄ
ይሄው ከትቤያለሁ ልቤ ውስጥ አርቅቄ
እንድትፈርድ እያት
የአንገቷን ጠረን በምን ልሳላት?
የማይተው ሆኖ ክፉ ዝቋን መግለጥ
እስኪ በል ንገረኝ ምን ከምን ልቀይጥ?
ከሸራዬ ሸራ የሷን ድምፅ መስማት
ምን ይሉት መቀደስ እንዴት ያለ ምትሀት
የዕድሜ ልክ እርግማን ሴት የመሳል ምክንያት!!!
መልስ አልባ ጥያቄ
ሀዘንተኛ ሳቄ
ያውም በኮሳሳ በደሳሳ ጎጆ
ከየዋህ አፍቃሪ ብርታቱን ኮርጆ
ሽንቁሩ በበዛ በተሰበረ በር
ከነብሴ ሚነጣ ውብ ሸራ መወጠር
ከደሜ ቀይ ቀለም ከላቤ ወዝ መንከር
ከድሜ እየቀነሱ እሷ ላይ መከመር
በነገረ ነብሷ ጠልቆ መመራመር
በቃል ኪዳን አስሮ ቀለማት ማጋባት
እ…ሰይ…!! ብዙ ብሎ ንግስናን መቀባት
ከዚያ … …
ከቆሙበት ብሩሾችን ማንሳት
እልባት እስኪገኝ ላመታት መረሳት
ከሸራው ምስልሽን ከምስልሽ ላይ አንቺን እያነቡ … መቅደድ
ወደ ማይታወቅ ወደ ሩቅ መስደድ
ቀለማት አርግዘው ቀለም እስኪወለድ
ምስልሽን ሚተካ፣ ዓይን ሚሞላ ውበት፣ በጣት የሚነካ፣ ህብር ቅኔ እስኪገኝ
ምስልሽና ነብስሽ ከሸራ እስኪገናኝ
ውበትሽን ሸርፌ አላጓድልሽም
እስከጊዜው ድረስ ተይኝ አልስልሽም!!!
…….//……

Published in የግጥም ጥግ
Monday, 25 November 2013 11:30

አባ ወራው…!

…ጨረቃዋ አጠገቧ ያሉትን ከዋክብቶች…እንደጠጠር ልቅም አድርጋ ቅልልቦሽ የምትጫወት የገጠር ልጃገረድ ትመስላለች፡፡ ሳቋ አይፎርሽም፡፡ መልኳ ግን ያልታጠበ የድሃ ትሪ አይነት ነገር ነው፡፡ (ልጅ ሆነን ማርያም ልጇን አቅፋ ትታያለች የምንላት አይነት አይደለችም)
አቶ ባይጨክን…ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ይጋርዱሽ ጋር በረንዳ ላይ ተቀምጠው የጋለ ወግ እየጠረቁ ነው፤  ቀድሞ የነበረው ንዴታቸው በመጠኑም ቢሆን በረድ ያለ ይመስላል…አንጋጠው ጨረቃዋን በትዝብት እየገረመሙ ወሬአቸው ለባለቤታቸው ይሁን ለጨረቃዋ ሳይለይ ያወራሉ… “እቺ ሐገር ሰው አጥታለች፤ እስቲ ይሁን…ተቆርቋሪ የሌላት ቤተክርስቲያን መሆኗም አይደል…ጉድ እኮ ነው ጽናጽሏን ሲወስዱ፣ ከበሮዋ ለዳንኪራ ሲደለቅ፣ በገናዋ ለአለም ሙዚቃ አስረሽ ምችው ማጀቢያ ሲሆን…መቋሚያዋ እንደ ጥምቀት ሽመል ሲቆጠር…ተው የብቻችን የሆነውን አትንኩ! የሚል ጠፋ፤ አሁን ደግሞ ጭርሱኑ ጠቅለው የራሳቸው ሊያደርጓት አሠፈሠፉ”
ወ/ሮ ይጋርዱሽ ሙሉቀን ይዘውት የነበረውን ሰፌድ ከነስንዴው ከአጠገባቸው ለማንሳት እየቃጡ ነበር…የባለቤታቸው መብሰክሰክ የጤና አልመስል ቢላቸው፣ ሰፌዱ ላይ ያለውን አንስቶ ከማስገባት ባለቤታቸውን ይዞ መግባት አንገብግቧቸዋል፡፡ እህል አይደሉ እፍስ አርገው አያስገቧቸው … ጨንቋቸው አብረው አንጋጠጡ፡፡ “ባያስቆጡን፣ ባያስኮርፉን ምናል?!” እያሉ መቆጨታቸው አሁን እሳቸውንም ሳያውቁት እየቆጠቆጣቸው ነው፡፡
“እንደው የቲቶ አባት … ሙሉቀን እንዲህ በንዴት መቃጠል ምን ሊረባዎ ነው? አንዳንዴ መልስ የሌለው ጥያቄ እያመጡ ግራ ገብትዎት እኔንስ ግራ ባያጋቡኝ ምናለበት...”
“አንቺ ምንሽ ተነካ! ከእነ ልጆችሽ ተረት ተረት ወይም ኩምክና የማወራ እየመሰላችሁ፣ ሳቃችሁ ጣሪያ ነክቷል…! እንዴት ሰው አንድ ተቆርቋሪ ያጣል!?”
“አይ…እርስዎ ደግሞ ከእኛ ከፍ ያሉት መመለስና “ሐይ” ባይ ያጡለትን እርስዎ ብቻዎትን ሊወጡት ነው…ደግሞስ ራሱ ባለቤቱ አንድዬ ዝም ያለውን እኛ ምን ቤት ነን”
“እምትተኚ ከሆነ ገብተሽ ተኚ…ቆመሽም አላማረብሽ”
“እርስዎስ?” ወ/ሮ ይጋርዱሽ የተለየ ስሜት ተሰማቸው፡፡
“ከጨረቃዋ ጋር እማወራው አለኝ…ቢያንስ ሐሳቤን ባትደግፍ አትነቅፈኝም”
አገጫቸውን አስደግፈው በተከዙበት ምርኩዝ መሬቱን በቁጭት ደቀደቁ!
ከአሮጌው ጣውላ የሚወጣው ድምጽ፣ የአቶ ባይጨክንን መትከንከን ይበልጥ ቅላፄና ውበት ሰጠው፡፡
“አይ እንግዲህ ይገቡ እንደሁ ይግቡ…ምነው እቴ!”
ወ/ሮ ይጋርዱሽ የባላቸውን ፀባይ ያውቃሉ…የውሸት ቆጣ ሲሉባቸው ሁሉንም ነገር ተወት አድርገው ወደነበሩበት እንደሚመለሱ፡፡ ዛሬ ግን መረር ያለ ሆነባቸው፡፡
“ነገርኩሽ እኮ ሰሚ ሰው ከሌለ፣ ከፈጣሪ የእጁ ስራ ጋር ባወራ ምናለበት?”
“ምን ቸገረኝ ብርዱ ሲቆነድድዎ ይገቡ የለ…ኋላ እዚህ ጋ ወጋኝ፣ እዚህ ጋ ቆረጠመኝ፣ እሺኝ ቢሉ…ድቆሳ እንደሚጠብቅዎ አይዘንጉ…” አፋቸው በተናገረው ውሸት ሆዳቸው እያዘነ፣ ትተዋቸው በሠፌዱ ላይ ያለውን እህል የተለቀመውን ካልተለቀመው ደባልቀው ገቡ፡፡ አቶ ባይጨክን ሽቅብ አንጋጠው ቀሩ፡፡
ወ/ሮ ይጋርዱሽ በባለቤታቸው መጨከን ስላልቻሉ ጋቢ ይዘው ወጡ…“ጦሱ ለእኔው ነው የሚተርፈው…” ጋቢውን ነጠል አድርገው ከትከሻቸው ላይ ደረቡላቸው…እሳቸው የለበሱትን ነጠላ ጋቢ ደግሞ ለሁለት አጥፈው ጉልበታቸው ላይ ጣል አደረጉላቸው፡፡
“ነፍሴን እምነት እየበረዳት ሥጋዬን ሸማ ብታለብሽው እንደምን ሊሞቀኝ?”
አሁንም በአይናቸው ስለት ሠማዩን እንደወጉ ናቸው፡፡
“አይ እንግዲህ ምነው አይፈላሰሙብኝ…ጃጁ ልበል እርስዎ ሰውዬ?”
የተላጠ ትሪ የመሰለችዋ ጨረቃ እየደመቀች እየደመቀች…ኮከቦቹ በድምቀቷ ተሸማቀው ከአጠገቧ እየራቁ እየራቁ ለመጥፋት ተቃርበዋል፡፡
“ግቢ እስቲ ይበርድሻል?”
“ለእኔ ማሰቡን ትተው ለራስዎ በተጨነቁ”
“ተይኝ አልኩሽ እኮ!” አሁንም ጨረቃዋን ሠርስረው አፈጠጡባት…ድንገት የውጪው በር “ቃ” ብሎ ሲከፈት የሁለቱም ዓይኖች እኩል ዞሩ…ቲቶ ነበር … እናትና አባቱ በረንዳ ላይ ሆነው ሲያያቸው ፍቅር እደሳ መስሎ ተሰማው መሠለኝ ገና ከበር ጥርሱን ፈልቅቆ ቀረባቸው፤ “እንዴት አመሻችሁ ጐረምሶቹ?” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ሳቃቸው ቀደማቸው፡፡
“እንዴት አመሹ ሽማግሌው?” ለቀልዱ ቀልድ ወረወሩለት፡፡
“የምን ትዝታ እየቆሰቆሳችሁ ነው?”
“አባትህ የድሮው ትዝ አላቸው መሰለኝ አልገባም ብለውኝ እርሳቸውን እያባበልኩ ነው”
“አውርጄ ካልሠጠሁሽ እያለ እንዳይሆን ጨረቃዋን? አባዬ እንደምን አመሸህ?”
ምርኩዛቸውን ባገጫቸው ተደግፈው በራሳቸው ሃሳብ ተመስጠዋል…
“አባዬ እንደምን አመሸህ? ስላመሸሁ ይቅርታ?” ሰምተው እንዳልሰሙ መልስ ነፈጉት፡፡
“ተዋቸው እስቲ…እርጅና የተጫጫነው አዕምሮ ቶሎ አይነቃም!”
“የጥቅምት ብርድ እንኳን የእናንተን የወጣቶቹን ገላ አይደለም እኛ ሥንት ያየነውንም ያንሰፈስፋል…በሉ ግቡ…” ቲቶ ሳቁ አምልጦት የእናቱን ትከሻ ተደግፎ ተንፈቀፈቀ …
“ከዚህ አይዘልም የእናንተ ቧልት! እየሳቃችሁ የእጃችሁን ታስነጥቃላችሁ”
“እስቲ እሺ ካሉህ … ይዘሃቸው ግባ” አባትና ልጅን ትተው ወደ ውስጥ ገቡ፡፡
ቲቶ የአባቱን መተከዝ ተመልክቶ በግድ አስነስቶ ይዟቸው ገባ፡፡
ጨረቃዋ…የተላላጠ ፊቷን እያወዛች…ያለስንቅ እንደሚጓዝ መንገደኛ ቀስ እያለች ጉዞዋን ቀጠለች…
*   *   *
በጅማ ረከቦት የታዘለው ስኒ ንጣቱ የወተት ጥርስ የመሰለ ነው፡፡ ወ/ሮ ይጋርዱሽ ተርከክ ያለው እሳት ላይ ተጥዶ የሚንደቀደቀደውን ቡና እንዳመል እንዳመሉ ቀንሰው፣ በያዙት ቡና መንደቅደቁን እያባረዱ … በደንብ ካንተከተኩት በኋላ አወረዱት፡፡ አቶ ባይጨክን ከቤተ እግዚአብሔር እንደተመለሱ ወዲያው ነበር ቁርሶ የቀረበላቸው፣ እንደነገሩ ቀመስመስ አድርገው የሚወዱትን ቡና እየተጠባበቁ ነው፡፡ የማታው ስሜታቸው አሁንም በልብና በፊታቸው ላይ ደልደል ብሎ እንደተቀመጠ ያስታውቃል፡፡
ቲቶና ሁለቱ እህቶቹ ከመኝታ ቤት እየተሳሳቁ ሳሎን ከወላጆቻው ጋር ተቀላቀሉ …አባታቸው የበፊት ሳቂታ ፊትና ተጫዋችነታቸውን ባደራ በሊታ እንደተነጠቁ ዝም ብለዋል፡፡ ልጆቹ የተለየውን ዝምታ ተመልክተው የሆነ ነገር እንደተፈጠረ ከማታው መነሻ አሁን ደመደሙ፡፡ ሁለቱ ሴቶች ተቻኩለው አባታቸው አጠገብ ተቀመጡ፡፡
ቲቶ ነገሩን በግርምት ቃኝቶ ያለወትሮው እንዲህ ውርጭ የመታውን የቤቱን ሰላም ለመመለስ ከእናቱ አጠገብ ተቀመጠ፡፡ “እስቲ ራቅ በል አመድ ይቦንብሃል”
“ተይው… አመዳም ፊት ላይ አመድ ቢነሰነስ ብርቅ ነው እንዴ?”
“አመዳም መሆንህን ማወቁ በራሱ ትልቅነት ነው…” አባቷ አጠገብ የተቀመጠችው ታናሹ ፈትለወርቅ ነበረች፡፡ “አንቺ የግድግዳ ጌጥ … አገልግል የመሰልሽ ልጅ ዝም አትይም?” በቀኝ በኩል ያለችው ስርጉተ ማርያም፤ የአባቷን እጅ እያሻሸች የሚሆነውን አይኗን ከብለለል እያደረገች ትመለከታለች፡፡
“እስቲ ቡናውን በፀጥታ እንጠጣበት…ይሄ መልክ የሌለው ቀልዳችሁን ቀነስ አድርጉት…” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ቡናው እንዲሰክን የጀበናውን አፍንጫ ዘቅዘቅ አድርገው አስተካከሉት፡፡
“እማዬ ደግሞ ቤቱ ሰው የሌለበት እንዲመስል ፈለግሽ?” ፈትለወርቅ ቁንጥንጥ እያለች አባቷ ላይ ተጣበቀች፡፡
“እናንተ ልጆች፤ ከግራ ከቀኝ አጣበቃችሁኝ እኮ!” የአቶ ባይጨክን ድምጽ በኩርፊያና ቁጣ እንደታፈነ ያስታውቃል፡፡
“አባዬ ምን ሆነህ ነው?” ፈትለወርቅ እጃቸውን እየዳበሰች ይሁን እያፍተለተለች ባለየ መልኩ ጠየቀቻቸው፡፡
ስርጉተማርያም የአባቷ ደጋፊ መሆኗ የታወቀ ነው፡፡ “እስቲ ተይው ዝም ካለ ዝም ነው!”
ቲቶ በአይኑ ተቆጣት፣ ስርጉተማርያም “አልገባኝም” አይነት አፍጣ በአይኗ ጥያቄ ወረወረችለት፣ ቲቶ ለፈትለወርቅ “አዋሪው” አይነት በምልክት ነገራት፡፡
“አባ…ማታም ተቆጥተህ ግቡ አልከን…አሁን እሺ ስሞትልህ ምን ሆነህ ነው? ሳናስበው አስቀየምንህ እንዴ?”
አቶ ባይጨክን ሁሉንም ከገረመሙ በኋላ፤
“አሲዳም ዘመን! አሲዳም ዘመን ላይ ትጥለኝ አምላኬ!” ቀና ብለው ጣሪያው ሥር ያለ ይመስል ፈጣሪን ተመለከቱት፡፡
“ዘመኑ ደግሞ ምን በደለ…?” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ለጨዋታው ብለው ነበር፡፡
“ኤዲያ! ዘመኑ ነው እንጂ እንቅልፋም፣ ትውልድ ተሸክሞ እሹሩሩ የሚል…”
“ተሳስተሃል አባዬ…ትውልዱ ነው እንቅልፋም ዘመን ለማንቃት እየጣረ ያለው…”
ቲቶ ማውራታቸው በመጠኑም ቢሆን ደስ ብሎታል፡፡
“ያው ነው ቀልቀሎ ሥልቻ ስልቻ ቀልቀሎ!” ሳያስቡት ገንፈል ገንፈል አሉ፡፡
“ታዲያ ምን ያስቆጣዎታል? እርስዎ ሰውዬ ሲያበዙት ደግሞ አይታወቅዎትም…እርስዎ የፈለጉትን ሰው ካልተከተለ ትክክል የሆነ አይመስልዎትም ልበል…”
“አንቺ ሴት…በቤታችን ህገመንግስት መሠረት ባንቺ የእምነት ነፃነት (አስተሳሰብ) ጣልቃ አልገባም፡፡ በእኔም የእምነት ነፃነት ማንም ጣልቃ መግባት የለበትም”
የለበሱት ጋቢ ተንሸራቶ ሊከዳቸው ሲል፣ አጣፍተው ከትከሻቸው አደረጉት፡፡
“ድሮውንስ በእኔ መብት ሊገቡ ያምርዎት ነበር? ወቸው ጉድ … ይጋርዱሽ እያደርሽ እማትሠሚው ጉድ የለ” ቤቱ አዝሎት የነበረውን ቀዝቃዛ ውርጭ በሳቃቸው ድራሹን ለማጥፋት ይመስላል…እሚያስቅ ሳቅ ሳቁ፡፡
“እስቲ እንካ ቲቶ … የቡና ቁርስ አሲዝልኝ” ቲቶ የዘረጉለትን በቀለም ያጌጠ እርቦ ተቀብሎ፣ መጀመሪያ ለአባቱ ዘረጋ “በቃኝ!” አሉት በእጃቸው፡፡ ሁለቱም እህቶቹ እኩል በእናት እጅ የተገመደለውን አምባሻ አነሱ፡፡
ፈትለወርቅ ከያዘችው ላይ ቆርሳ ለአባቷ በግድ አጐረሰቻቸው “አባባ የታወቀ ነው … በማንም የእምነት መብት ጣልቃ ገብቶ አያውቅም!”
“ድሮውንስ ሊገቡ ያምራቸው ነበር” ከቲቶ ጋር ስምም የሆኑ ያህል በአይን ተግባቡ፡፡ ልጆቹ የአባታቸውን፣ እሳቸው ደግሞ የባላቸውን ከድብርት መውጣት ፈልገዋል፡፡
“ማን ወንድ የሆነ ነው መብቴን የሚገፍ!” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ድጋሚ የቀልድ ትኩስነታቸውን አወጁ… “አልገባም እያልኩሽ አትሰሚም” ቀዝቀዘዋል፡፡
“ማሰብዎ በራሱ ጽንፈኝነት እያውጠነጠኑ እንደሆነ ያሳብቅዎታል”
“እየው እንግዲህ … ነገሩን ሁላ ፖለቲካ ስታደርገው…”
“ሞኝ ንዎ ልበል …እያንዳንዷ ፖለቲካ መጠንሰሻዋ መኖሪያ ቤት እኮ ነው … ከቤት የተጠነሰሰ ፖለቲካ እኮ ነው ሀገሬው የሚጠጣው፡፡”
ልጆቹ፤ የእናትና የአባታቸውን የቃላት ልውውጥ የጠረጴዛ ቴኒስ እንደሚመለከት ሰው፣ አይናቸውን ከወዲያ ወዲህ እያንከባለሉ በጥምር ያያሉ፡፡ ሁሌም የእናትና የአባታቸው ጨዋታ ትምህርት ቤታቸው ነው፤ መከባበርን፣ መፋቀርን፣ ይማሩበታል…
“ነግሬሻለሁ … በቤታችን የእምነት ህግ መሠረት፣ የፈቀድሽውን እና የወደድሽውን ማመን መብትሽ ነው፤ እኔ ባልሽ የልጆችሽ አባት እንጂ ባላንጣሽ አይደለሁም … ስለዚህ “ጣልቃ ገብነት” የሚባለው ክፉ ደንቃራ ህሊናችን ውስጥ መታሰብ የለበትም…በልዩነት ተስማምቶ መኖር ይቻላል፡፡”
“ደንቡን መጣስ ከአክራሪነት ያስመድባል…” አሁንም ከት ብለው ሳቁ፡፡
“ምን ካለበት የተጋባበት”… እያሉ ተፍነከነኩ፡፡ ኩልል አድርገው የቀዱትን ቡና ነጭ ጥርስ በመሰለው ስኒያቸው ቀድተው ቲቶን አስነሱት፡፡
ሁሉም አቦል ቡናውን ሳይሆን ወሬውን የሚጠጣ ይመስል በችኮላ ጨልጠው ስኒዎቹን መለሱ፡፡ ወ/ሮ ይጋርዱሽ ስኒዎቹን አጠገባቸው ካለው የኮኮስ ጣሳ እየነከሩ ካለቀለቀቁ በኋላ ረከቦቱ ላይ ደረደሩ፡፡ በመጠኑ ፀጥ ያለውን አየር ለመገርሰስ ይመስላል ስርጉተማርያም “እማማ ያለችው የበላይ አካሉን ደንብ አለማክበር … ከአክራሪነትም ያስመድባል ነው”
አቶ ባይጨክን ስርጉተማርያምን ገርመም አድርገው “ይሔው ነው እንግዲህ … ላልመጣ በሽታ መጀመሪያ ክትባት ብለው በሽታውን እንድንለማመድ ትንሹን በሽታ ይወጉናል፣ ያኔ ከውስጣችን ጋር ተስማምቶ ይኖራል፤ ህይወትም እንዲሁ ናት…ትንሿን ጥያቄ ስንፈራ ለትልቁ ወገቤን እንላለን፣ እንጂ የመጠየቅ መብቱ የለንም…በትንሹ ትልቁን ተለማምደነው…ጭቆና ተስማምቶን ‘አሜን’ ይሆናል ባህሪያችን፡፡ ያኔ የማንም መፈንጪያ እንሆናለን፡፡”
ፈትለወርቅ መልሳ የአባቷን እጅ ያዘች … በፍቅር ነው ያቀፈችው፡፡ አባቷ ያወሩት የሁላቸውም የውስጥ ጥያቄ ነው… “አባባ እውነቱን ነው …” አፏን ለእውነታቸው አላቀቀች፡፡ “ተያቸው ልጄ … አሁን አንገቴን ለሰይፍ … ደረቴን ለመድፍ የምሰጥለት ጉዳይ መጥቷል … ከዚህ በላይ መታገስ አይሆንልኝም!?” ወ/ሮ ይጋረዱሽ ሰረቅ አድርገው ተመለከቷቸው … “አቤት አቤት አልቀረብዎትም … በያዙት ጭራ ለዝንብ እማይጨክኑ ለምኑ ነው አንገትና ደረት የሚሰጡት?”
“ሙያ በልብ ነው! ወትሮም መሞት እንጂ መግደል አላማችን አይደለም!”
“እኮ እንዴት እንዴት?” የባለቤታቸው ምሬት እሚጋባ መሰላቸው፡፡
“የንቦቹን ቀፎ በጭስ አስክሮ ማሩን ለመውሰድ ቢቃጣም … ንቦቹ በጭስ አይበረግጉም!…እኛን የፈጣሪ ጭስ አፍኖ ካልገደለን በቀር…” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ይሔን አባባላቸውን ማስጨረስ አልቻሉም፡፡
“እንደው እርስዎ ሰውዬ ምናባቴ ባረግዎ ነው የሚሻለው?” ልጆቹ በድራማው ተመስጠዋል… “ብለው ብለው የፓርቲውን ምልክት በሰበብ አስባቡ ማስተዋወቅ ጀመሩ ማለት ነው?”
“አይ ሞኞ!” አቶ ባይጨክን ሙሉ በሙሉ ወደ ባለቤታቸው ዞሩ፡፡
“ንብን ለእነሱ ብቻ በውርስ የሠጠው ማነው? ነገሩ ወዲህ ነው ባክሽ… ለትንሿ ዝምታችን ስንብሰከሰክ፣ ትልቁ ላይ ልባችን ፈሠሠ!”
“አይ ወዲያ የምን አማርኛ እያወሩ አለመግባባት ነው” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ገብቷቸው እንዳልገባቸው የመሰሉት፣ ዝም ካሉ ባለቤታቸው ተመልሰው በቁዘማ ቆፈን ስለሚቀየዱ ነው፤፡፡“እውነትዎን ነው” ካሉ ጨዋታው ፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ ይሆናል። ዝም አስባዩ ዝምታ ደግሞ በቤቱ ላይ እንደልቡ ይፈነጫል፡፡
“እውነት ስትጮህ እምነት ስትገፋ፣ ለሌሎች ቅዠት ይመስላል…”
“አባባ፤ ሃይማኖት እኮ ፈሪዎች የሚሸሸጉበት ተቋም ነው፤ በዚህ በዲሞክራሲ ጊዜ ሐይማኖት ጥያቄ ሆኖ መቅረብ የለበትም፡፡” አለ ቲቶ፡፡
“አበስኩ ገበርኩ! ምነው ሞቼ ባረፍኩት! መቸም ባየ በሰማ አይፈርድም እንጂ የሰማዩ አባቴ እንደው በመብረቅ ፍግም ቢያደርግልኝ ምን ነበር…”
ሁሉም ግማሽ ሳቅ ሳቁ…ስርጉተ ማርያም ነገሩን ለማሟሟቅ ይመስላል…
“ቲቶ እኮ እውነቱን ነው አባዬ…”
“ይሔን ብሎ ቲቶ … ቡቱቶ ነው! ሃያ ሶስት አመት ሙሉ እሹሩሩ ያልኩህ በቂ ነው … ከዚህ በኋላ ቤቴን ለቀቅ! ራስህን ቻል!” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ሲስቁ … ሁለተኛውን ለመቅዳት ያነሱት ጀበናቸው ከእጃቸው አምልጧቸው ነበር፡፡
“አባዬ…”
“አትጥራኝ…” ቁጣቸው ፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡
“አባ…ዘመኑ የመሰማማት እና የመስማማት ነው…”
“ድንቄም የመሰማማትና የመሥማማት!” አፈጠጡበት፡፡
“ቢሆንም እየውልህ … እቺ ሀገር የሚያምርባት ፀጥ ብላ ልማቷን አፋጥና … ካደጉት ሀገር ተርታ መመደብ ነው እንጂ በውስጧ የተሰገሰጉት በእምነት ጥላ ተጠልለው ሽብርተኝነትና አክራሪነትን እሚያቀነቅኑ ቀንዳቸውን ቢያሾሉም እኛ ከመስበር ወደኋላ አንልም!”
“ምን ማለት ነው ሽብር? … ምንስ ማለት ነው አክራሪነት? እኔ ገንዘቤን ሐይማኖቴን አጥብቄ ካልያዝኩ ምኑ ላይ ነው ሰውነቴ? ማጥበቄ ነው ማክረሬ?!” ቁጣቸው እሚበርድ አይመስልም፡፡
“በእምነት ሽፋን ሀገር ማፍረስን ምን አመጣው?” ወ/ሮ ይጋርዱሽ በወሬው ተመስጠው የቀዱት ቡና ቀዘቀዘ፡፡
“ይሁና…” ስርጉተማርያም አንገት ላይ የታሰረውን ማተብ እየዳበሱ… “ያለሙት የማይሆነው፣ ያሰቡት የማይሳካው … ዳኛ ስለሆንን ሳይሆን ፈጣሪ ስላልፈቀደ ነው፤ እባብን ረግጠው … አንበሳን አዘው … አምላካቸውን ቀን ከሌሊት በፀሎት የሚለምኑት የቅዱሳን ፀሎት ለጨካኞች አሳልፎ የሚሰጠን ይመስላችኋል? አትሞኙ! ‘ለአመፀኛ ህዝብ አመፀኛ መንግስት ያዝለታል’ ይላል፡፡ የሆነው … የሆነው እንዲሆን ሆኖ ነው፡፡”
“እየው አባዬ … ደግሞ ዙረህ ዙረህ ነገሩን በሙሉ ፖለቲካ ታደርገዋለህ… አሁን መንግስት እዚህ ነገር ውስጥ ምን አገባው?” ተለሳልሰው ሽርተቴ ገቡባቸው…” እኔ ምለው…የዚህ ቤት ሐይማኖት ምንድነው?” ሁሉም ፀጥ አሉ “መልሱልኝ እንጂ?!” አቶ ባይጨክን የምር ተቆጡ፡፡ ከተቀመጠበት ተነሱ፤ ፈትለወርቅ ቀና ብላ አየቻቸው፡፡ ስርጉተማርያም የሆነ ርህራሄ ልቧን ጐበኘው፡፡
“አባ፤ ያንተ እምነት ነው የኛም እምነት…” ስርጉተማርያም ነበረች
“እኔ ስላመንኩ ሳይሆን መርምራችሁ ማመን አለባችሁ!”
“ያባቴንማ አሳልፌ አልሰጥም!” ፈትለወርቅ ሳታስበው ተንገፈገፈች
“ፉከራ አታድርጊው … እምነት ማመን ነው! የሌላውን ሳይነቅፉና ሳያንቋሽሹ የራስን ብቻ ማመን አጥብቆ!”
“አባዬ፤ ዲሞክራሲ’ኮ የለገሰን ነፃነት፣ የፈለግነውን እንድንከተል ነው…” ቲቶ ነበር፡፡
“ሞኞ! የራስህን ስትከተል የሌላውን እየረገጥክና እያጥላላህ አይደለማ!” ዝም አለ ቲቶ
“እቺ ሀገር ሰው ትፈልጋለች…እናትና አባቶቿን እየናቀችና እየዘለፈች የትም አትደርስም! የአፍ ቅብብሉ በእውነት መለወጥ ይኖርበታል፤ በእምነትም ቢሆን እንደዛው! እውነቱ ታሽቶ መውጣት አለበት! እግር አጥበን የተቀበልናቸው ሁላ ዛሬ በእግራቸው ሊረግጡን አሰፍስፈው ይገኛሉ! እውነቱን፣ እምነቱን፣ መናገር ይጠበቅብናል…”
“ወጣም ወረደ እኛ የለገስናችሁ ነፃነት የዲሞክራሲያችን ነፀብራቅ ነው፡፡”
“ጣቃ ይመስል አትቀደድ! ለእኔ ነፃነት የለገሰኝ ያንተ ነፃነት ሳይሆን መስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሞቶ ህይወቴን ያወጀው መድኃኒዓለም ነው፡፡”
“ይኼ የድክመት መሸፈኛ ነው” ከእናቱ ጋር ተጠቃቀሰ፤ ቲቶ፡፡  
“ተወው እስቲ…ማጣፍያው ያጠረ እለት ‘ወይኔ’ ቢሉ ዋጋ የለውም!”
“የቲቶ አባት … መቋጫ የሌው ነገር አይተርትሩ … ‘ዝም አይነቅዝም”
“እድሜና ጤና ይስጣችሁና የሚታየውን እዩ … ሌላ ምን ልበላችሁ … የራስን መጠየቅ፣ ማስከበር ወንጀል አይደለምና ጠይቁ!”
ልባቸውን በተከፈተው መስኮት ፊትለፊታቸው ካለው ተራራ ላይ ላኩት …
ልጆቹና እናታቸው … በአባታቸው ምሬት አዘል ንግግር ግራ ተጋብተዋል …
ቀልድን ሲቀልዱት የልብን እውነት ሸርሽሮ ይጥላል፡፡ ከዝምታ ማውራትን መርጠዋል፡፡ ዝም እንዲሉ … እነሱም ዝም አላሉም፡፡

Published in ልብ-ወለድ

          ፍሬድሪክ ኒቼ አወዛጋቢ ከሚባሉት  ፈላስፎች መካከል የሚመደብ ሲሆን ሁሉንም የማፈራረስ አባዜ ብቻ ሳይሆን እራስንም የማፍረስ “ስንኩልነት” የተጠናወተው ነው። ቋሚ፣ነባራዊ፣ዘመን የማይሽረው የሚባል ጉዳይ ለኒቼ ትርጉም አይሰጡትም። ምናልባትም ለኒቼ ትርጉም የሚሰጠው ከቅድመ ሶቅራጥስ ፈላስፎች መካከል ሔራክሊተስ የተባለው ፈላስፋ ያቀነቅነው የነበረው “ሁሉም ነገር መቆሚያ በሌለው ለውጥ ውስጥ ነው…” የሚል ትምህርት ነው፤ “በአንድ የወንዝ (ውኃ) ሁለቴ መሻገር አንችልም” ይለናል ሔራክሊተስ፤ ምክንያቱም ተመልሰን ስንመጣ ውኃው ይለወጣልና። እንዲህ አይነት ቅርጽ የሌላቸው ለውጦች በኒቼ የፍልስፍና ድርሳናት ውስጥ እንደ “ከብት የዋለበት ማሳ” የፍልስፍና ፍሬ ሐሳቡን አተረማምሰውት ይገኛሉ።
ከሉተራዊያን ቤተሰቦች በጀርመን ሃገር ሮክን ከተማ የተወለደው ኒቼ፤ በልጅነቱ አባቱ ስለሞቱበት በእናቱ፣ በእህቱ እና በአክስቱ ተከብቦ እንዳደገ ይነገራል። በፊሎሎጂ ትምህርቱ ጀት ተማሪ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን በሃያኛ አጋማሽ እድሜው ላይ  በባዜል ዩኒቨርሲቲ በፕሮፌሰርነት ይሰራ ነበር። በእርግጥ The Birth of Tragedy የተሰኘው የመጀመሪያ ስራው የተጠበቀውን ያህል አድናቆት አላስገኘለትም፤እንዲያውም ለሰሉ ትችቶች ዳርጎታል። የእነ አኪለስን እና ሶፎክልስን ድራማዎች ተራራ ላይ እየሰቀለና የአፍላጦንን ስራዎች ግን መቀመቅ እየከተተ፤በእነዚህ ስራዎች የግሪክን መነሳትና መንኮታኮት ያነፃፅራል- Birth of Tragedy በተባለው ስራው። ከፈላስፎች ሁሉ ኒቼ  የሚለየው በግልጽና ቀላል ቋንቋ  የፍልስፍና ስራውን በማቅረቡ ነው፤ በተለይም ከነ ካንት ጋር ስናነጻጽረው ምን ያህል ሐሳቡን በቀላል መንገድ ለማቅረብ እንደተጋ እንገነዘባለን።
ኒቼ በባህሪው አመጸኛ ህጻን ልጅ ይመስላል፤ ያውም ከአባቱ ጋር ያለ አቅሙ እልህ ውስጥ የሚገባ  ህጻን። “እግዚአብሔር ሞቷል” ይለናል። “እንደ ገደልነው እረሳችሁት እንዴ?!’’ በአንክሮ መልሶ እየጠየቀን።  ሐዋርያው ቶማስ፤ ክርስቶስ ከመቃብር መነሳቱን አላምንም ብሎ የተቸነከረ ሰውነቱንና  በጦር የተወጋ ጎኑን በመዳሰሱ ምክንያት፤ እንደ እርሱ ካላዩ የማያምኑ ሰዎች ባገራችን “ቶማሳዊያን” ይባላሉ። ደረቅ ማስረጃ ይሻሉና። ኒቼ ክርስቶስ መሞቱን እንጂ መነሳቱን አይቀበልም። መሞቱን  በስብከት(ከመጽሐፍት) ተቀብሎታል፤ ከመቃብር ለመነሳቱ ግን በስብከት ብቻ ማመን አልፈቀደም። ክርስቶስ   ከመቃብር እየተነሳ “ማርያም” ብሎ ማርያም መግደላዊትን በስሟ እንደ ጠራት ሁሉ “ኒቼ” ብሎ እንዲጠራውና ከመቃብር የተነሳውን ሰውነቱን እንዲያሳየው ይሻል። የዋህ ኒቼ!
ለሰው ልጅ ትልቅነት፣ ክብር፣ ፌሽታ……የኒቼን ያህል የሞገተ ፈላስፋ ያለ አይመስለኝም። መስከር፣ መጨፈር፣ መውደቅ፣ መነሳት……ይህ ሁሉ ለኒቼ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ውበቱ ነው። ደግሞ እንደገና ከወደቅንበት ስንነሳ፤ ሌላ ትልቅ ሰብእና! ልዕለ ኃያል ሰው መሆን! ይህ ነው የኒቼ ምኞት፤ ትልቅ ፣የትልቅም ትልቅ መሆን፤ እራስን በማንጻትና በቀና መንገድ በመጓዝ! እራሳችንን ባነጻን ቁጥር ደግሞ የትልቆች ሁሉ ትልቅ የመሆንን ጸጋ እንጎናጸፋለን፤ በማያቋርጠው የተፈጥሮ የለውጥ መዋቅር ውስጥ እየተጓዝን እራሳችንን የትልቆች ሁሉ ትልቅ ማድረግ። “ልዕለ−ሰብ”-Super/Over−Man።  ከትናንሽ ምድራዊ ሐሳቦች እራሳችንን አሸንፈን ልዕለ−ሰብ መሆን፤ እራስን ማንጻት ትልቅ የኒቼ እሴት ነው።
ኒቼ በፕሌቶ ስራዎች ስር አጮልቆ ሶቅራጥስን መሃል አናቱን በመዶሻ ይፈልጠዋል- እንዲህ እያለ “ይህ ዘመናዊ ዓለማችን በሔለናዊ (አሌክሳንድሪያዊ)ባህል ተጠፍሮ ተይዟል። እናም የኀልዮት፣የሳይንስ አገልጋዩ፣ባለ አዕምሮው ሰው እንደ ሁነኛ ሰው ይቆጠራል፤ ለዚህ ሁሉ አርአያና ቤዛ ደግሞ ሶቅራጥስ ነው።” ኒቼ ለሶቅራጥስ ያለው ንቀት መቼም አያድርስ ነው። በፌሽታ፣በደስታና በጭፈራ ይኖር የነበረውን የግሪክ(ዲያኖዚያን)ህዝብ፤ ሶቅራጥስ የሚሉት መጣና የግብረገብ ጥያቄዎችን እያነሳ ናላቸው እስኪዞር ድረስ በጠበጣቸው፤ ይለናል ኒቼ።
የዲያኖዚያን ግሪክና የአፖሎኒያን ግሪክ ለኒቼ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቁና የተቃቃሩ ዓለማት ናቸው። እውነት፣ውበት፣ትክክለኝነት ማለት የዲያኖዚያን የጭፈራ፣የስካር፣የዳንስ…ህይወት የሚወክል ነው። አፖሎኒያን ማለት ቅርጽ/ስርዓት መያዝ የምትፈልግ ተፈጥሯዊ  ያልሆነች አስመሳይ ህይወት ናት፤ለኒቼ። የግብረገብ ጥያቄዎች እራስን ለማሸማቀቅ የሚዳርጉን ተፈጥሯዊ ስላልሆኑ ነው ይላል። ተፈጥሯዊ ውበት የሞላበት ህይወት ማለት የዲያኖዚያን ህይወት ነው። የእነ ሶቅራጥስ/አፖሎኒያን እራስን እየመረመሩ የመኖር ህይወት፤ የኛ የውሸት ህይወት ነው፤ ለኒቼ። እንዲህ ነው እንግዲህ የኒቼ ነገር። አንድ ድርሳኑ ውስጥ የሞገተለትን ነገር በሌላ ድርሳኑ ውስጥ ብል እንደ በላው ጨርቅ ሙሽሽ ያደርገዋል። (ምናልባት ሳይጽፍልን የቀረ “the virtue of inconsistency” የሚባል ድርሳን በልቦናው ሳይኖረው አይቀርም።)
የሶቅራጥስን የስነ ምግባር ጠበቃነት እያጣጣለ፣ የራሱን መመሪያዎች እንድንከተል ይቀሰቅሳል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን ዝቅ ዝቅ እያደረገ የራሱን ወንጌል ይከትባል። የዘፍጥረት(ኅላዌ) ሐሳቦችን እያድበሰበሰ፣ የሰው ልጅ እንዴት ልዕለ ፍጡር መሆን እንደሚችል ይመክረናል። የኒቼ ሐሳብ እንደ ድቡልቡል ኳስ  ባሰኘው አቅጣጫ ነው የሚፈሰው። ያኛውን ውበት እርሱት፤  ውበት ማለት ይህ ነው ይለናል፤ የራሱን ምኞት እኛ ላይ እየጫነ። ሰው እንደ መንጋ ከብት እያሰበ ያፈለቀውን እውቀት መቀበል የለባችሁም፤ የራሳችሁን አተያይ በመፍጠር የራሳችሁ እውቀት ይኑራችሁ ይለናል። እውቀትን  ከቀደሙት መማር እንደሌለብን ቢመክረንም እውቀት እንዴት እንደምናገኝ ግን ፍንጭ አይሰጠንም፡፡ ነባርና የጃጁ የፍልስፍና ጥያቄዎችን ማንሳቱን ይዘነጋውና “ልማዳዊ ፍልስፍናን ከነውርሱ እርሱት፤ ምክንያቱም ፍጹማዊ ባህሪ የተጠናወተው ስለሆነ። ኔቼ የልዕለ−ሰብ ፍቅር ይኑረው እንጅ የልዕለ−እውነት አባዜ አይነካካውም። የአንድ ጊዜ እውነቱን ንዶ በሌላ ጊዜ ሌላ እውነት ሊሰብከን ይችላል። ይህ ለኔቼ እራሱን የቻለ ስልት ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም ነገር በማያቋርጥ የለውጥ ሥርዓት ተገዥ ነውና።
ሰማያዊ(transcendental)የሚባል እውነት መቼውንም አይኖረንም፤እያንዳንዳችን እንደየ አስተሳሰባችን የየራሳችን እውነት አለን እንጅ። ሁሉም ነገር የይምሰል ነው፤ ዛሬ እውነት የምንለው ነገር ለኑሯችን የሚረዳንና  ለክፉ ነገር የማይዳርገን ስህተት ነው። እራሳቸውን የቻሉ የብዙ ነገሮች ጥርቅም ናት ዓለማችን፤ የእርስ በእርስ ተራክቧቸውም(ጥምረት) አንዳች ህግን የተከተለ ነው፤ የምናስተውላቸው እኛም በአንጻሩም ቢሆን እራሱን የቻለ ሰብእና አለን። እኛ ሁላችንም የየራሳችን የስሜት ህዋሳት አሉን፤ አካባቢያችንን (ዓለማችንን) የምንመረምረውም በየራሳችን ስሜት ነው፤ ዓለምም የተለያዩ ነገሮች ጥንቅር ናት፤ያውም ደግሞ የራሳቸው በሆነ የተፈጥሮ ህግ እየተመሩ፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ከዚህ ውስጥ ዘላለማዊ፣አማናዊ፣ሰማያዊ የሚባሉ እውቀቶችን እና  እውነቶችን የምናገኘው፤ ይላል ኒቼ። እንዲች እንዲች ያለች ነገር ለኒቼ ቀልድ ናት፣ ልቦለድ።  ፈጽሞ አይቀበላትም።
ለዘመናት በፈላስፎች አምባገነንነት ተይዞ የነበረው “ፍጹም እውነት” የቋንቋ ገላጭነት እና ከሳችነት ችሎታ ላይ የተንጠለጠለ የአስመሳይነት ፉከራ ነው፤ ከማንኛውም የተግባቦት ክህሎታችን የተለየ አይደለም ይለናል ኒቼ። (ፊሎሎጂስቱ ኒቼ ብሩህ አእምሮውን እያሰገረው ነው።) ቋንቋን እንደ መግባቢያ በፍልስፍናችን ውስጥ መጠቀማችን ግድ ስለሆነ ከራሳችን ከውስጣችን ያለውን ቀጥታ ማውጣት አይቻለንም። በመካከላችን ቋንቋ ይኖር ዘንድ ግድ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ፍጹምና ቀጥተኛ የሚባል ሐሳብ ከውስጣችን ማፍለቅ አንችልም፤ ሁሉም በቋንቋ ተነካክቶ እጅ እጅ ያለ ነውና።
እውነትን ፈላስፎቹ እንደ ቅዱስና ምትሐታዊ ነገር አድርገው ያቀርቡልናል፤ ነገር ግን ተምሳሌታዊ ወይም ግርድፍ ማነብነብ ወይም የሆነ ግብ ለማሳካት ተብሎ የተዘወረ ነው ባይ ነው።
የኒቼ ውርጅብኝ በዚህ አያበቃም (በአማርኛ ቸግሮኛልና በፈረንጅኛ አፉ እንስማው) “It [truth] is a movable host of metaphors, metonymies, and anthropomorphisms: in short, a sum of human relations which have been poetically and rhetorically intensified, transferred, and embellished, and which, after long usage, seem to a people to be fixed, canonical, and blind. Truths are illusions which we have forgotten are illusions.”
በደርጉ ዘመን በነበረው ትምህርት፤ የዕደ ጥበባት ማዕከል የሚባል ክፍል በየትምህርት ቤቱ ነበረ፡፡ ታዲያ ጋሼ ምህረቱ የምንለው አንድ የትምህርት ቤታችን የማዕከሉ ኃላፊ ነበረ። በእረፍት ሰዓትና መምህር ባልገባልን ክፍለ ጊዜ ሮጠን ወደ ጋሼ ምህረቱ እንሄድና ወንበር ጠረጴዛ ሲጠግን/ሲሰራ መጋዙን ሲያስፏጫት እያየን መደሰት እናዘወትራለን፡፡ ልክ እንደርሱ መጋዟን ይዘን ገና ከእንጨት  ስናገናኛት አያያዙን አላውቅበት ብለን መጋዙ ይዘልና ወደ  እግራችን ወይም ወደ እጃችን እየመጣ ያስጮኸን ነበር። ጋሽ ምህረቱ ግን ጣውላ አሊያም እንጨት እየቆረጠ “ሽው… ሽው… ሽው” እያሰኘ መጋዟን “የምናውቅብሽ!” ይላል፤ድምጹን ደመቅ አድርጎ እኛን እያየ። የተካንኩብሽ ሙያዬ ማለቱ ነው። ኒቼም ከየትኞቹም ጽሑፎቹ በላይ የቋንቋ ፍልስፍና ላይ ሲደርስ “የምናውቅብሽ!” የሚል ይመስለኛል። በዚህ ረገድ የሚሰጠው ትችት ማንንም ፈላስፋ ቀና አያስብልምና።

Published in ጥበብ
Page 4 of 19