1 አፈወርቅ ገ/ኢየሱስንና ዘመነኞቹን ወደ ስዊዘርላንድ፣ ተክለሃዋርያት ተ/ማርያምንና ዘመነኞቹን ደግሞ ወደ ሩስያ በመላክ የተጀመረው የዘመናዊ ትምህርት ኀሰሳ፤ በአጼ ምኒልክ ታጋይነት መሠረት ሊይዝ ቢታትርም ብዙ መውጣትና መውረዶችን ዐይቷል፡፡ የምኒልክ ሕልም በልጃቸው በንግሥት ዘውዲቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ እውነተኛ ታሪኩ የማን እንደሆነ ባይገባኝም (ለተፈሪ መኮንን የሚሠጡ እንዳሉ ሆነው) ንግሥት ዘውዲቱ ያሠሩትን የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መርቀው ሲከፍቱ፣ እንዲህ መናገራቸው ተዘግቧል - ‹‹ ለኢትዮጵያ ነጻነትና ጽናት ወሰንዋን ጠብቆ፣ አሳፍሮና አስከብሮ ለማኩራትና ለህዝቧ ልብ የታመነ ኃይል እንዲሆነው ለማድረግ መሣሪያው ትምህርትን መማር ነው›› በንግሥቲቱ ንግግር ውስጥ የተቀመጡ ቁልፍ ነጥቦች ነጻነት፣ ጽናት፣ ለህዝብ ልብ መታመን --- የሚሉ ናቸው፡፡ ሀገሬ ሀገር ናት፣ ሀገሬ ማደግ ትችላለች ብሎ ማመን፣ ሀገሬ ሉአላዊት ናት ብሎ ማመን፣ ሀገሬ ለምዕራባዊም ሆነ ምስራቃዊ የማትንበረከክ፣ የማትወድቅ፣ የማታንስ ናት ብሎ ነጻነቷን ማመን፤ አልሰደድም እሰራለሁ፣ አልዋሽም እኖራለሁ፣ አልሸነፍም አሸንፋለሁ፣ አውቃለሁ ቀን አለኝ ብሎ መጽናት፤ አልሰርቅም፣ ጉቦ አልቀበልም፣ አልቀጥፍም፣ ሀገር አልሸጥም፣ ህዝብ ከህዝብ አላለያይም፣ አልከፋፍልም ማለትና ማድረግ--- ለህዝብ ልብ መታመን ! እነዚህን ነጥቦች ሳስብና የእስከዛሬውን የሀገሬን ዘመናዊ ትምህርት ጉዞ ሳስተያይ፣ ብዙ ጥያቄዎች ይፈጠሩብኛል፡፡ የንግሥቲቱ ንግግር ዘመናዊ ትምህርትን ለማስፋፋት የታገሉት አባታቸው ሐሳብ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠሩ ክፋት የለውም። ሰፋ ባለ አእምሮ ስናየው ደግሞ አጼ ምኒልክም የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ እንደመሆናቸው፣ ከቴዎድሮስ የተረከቡት ርዕይ እንደሆነ መረዳቱ አያዳግትም፡፡ በእርግጥ በዘመነ ቴዎድሮስ ከዘመናዊው ትምህርት ሁሉ የውትድርና ትምህርትና ጥበብ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት እንደነበር አጼው ከእንግሊዝ ጋር ጦር እስከመማዘዝ የደረሱበት ሀቅ ይነግረናል። በገዥዎች መፈራረቅና በጣሊያን ወረራ (ሁለገብ ደባ) የተነሣ የዘመናዊ ትምህርት ጉዞ ሲደነቃቀፍ ቆይቷል፡፡ ለሀገሪቱ የሚበጀው ይሄ መስመር ነው ብሎ ፖሊሲ ነድፎ ሃያ ዓመታት ሙሉ የተንገታገተው የኢህአዴግ መንግሥት ብቻ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ የመለስን እንጅ የምኒልክን ራዕይ የማስፈጸም ኃላፊነት የለብንም እንደሚለኝ ብረዳም ‹‹ነጻነት፣ ጽናትና ለህዝብ ልብ መታመን››ን የማያጐናፅፍ ፖሊሲ ማስፈጸም ግን ውጤት እንደማያመጣ ይገነዘባል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 

         2 አባት የጭንቀት ፊቱን አውጥቶ ከጎረቤቶቹ ጋር ይወያያል፡፡ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ልጁ ከቤት ከጠፋ አራተኛ ቀኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ጎረቤቶቹ ሊያጽናኑት የመጡት፡፡ ልጁ የት፣ እንዴት፣ ለምን እንደጠፋ መረጃ ሳይገኝ ሰንብቷል። የቅርብ ጓደኞቹ አሉበት የተባለ ቦታ ሁሉ ሲፈለግ አዲስ መረጃ ተገኘ፡፡ ሁለቱም ጓደኞቹ ታስረዋል፡፡ ለምን? አባት ምስጢር እንዳይወጣ ይጨነቃል፡፡ በግምት አምስት አመት የሚሆነው ልጁ፤ እግር እግሩ ስር ይንከላወሳል፡፡ ልጁ ቃል እየለቀመ ያዳምጣል፡፡ አባት የጎረቤቶቹን ጉትጎታ ተከትሎ አንድ ቃል ተነፈሰ፤ (የጠፋው ልጅ እና ጓደኞቹ የመነን ተማሪዎች ናቸው) “ትምህርት ቤት ውስጥ ጋንጃ ይዘው (ሲያጨሱ) ተገኝተው ነው” አለ፡፡ ይሄኔ ህጻኑ ጠየቀ ‹‹ጋንጃ ምድን ነው?›› ብስጭት፣ ተስፋ ማጣትና ቁጭት ተደራርበው የሚነበቡበት የአባት ፊት፣ ወደ ህጻኑ ልጅ ዘምበል አለ፡፡ ሊናገር ያልቻለው ግን ፊቱ የሚናገረው አንድ እውነት ነበር “እባክህ አትጨቅጭቀኝ… ደርሰህ ለምትዘፈቅበት” የሚል ዓይነት ስሜት፡፡ አሜሪካዊ ልብወለዶች ወይም ፊልሞች ላይ እያየን ጉድ የምንልባቸው ‹ጋጠወጥነት በትምህርት ቤት› ዛሬ የሀገራችንን ትምህርት ቤቶች ያስጨነቀ ይመስለል፡፡ ለቁጥጥር አይደለም ለማሰብ የሚከብዱና የሚዘገንኑ እውነታዎችን እየሰማን ነው፡፡ በተለይ ከተማ ውስጥ ያሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብዙ ወንጀሎች መፈፀምያ እየኾኑ ነው፡፡ የወሲብ ፊልሞችን በስልክና በአይፓድ ክፍል ውስጥ መመልከት፣ በየአጥሩ ጥጋጥግ ጫት፣ ሲጋራ፣ ኃሺሽ መጠቀም፣ ግቢው ከተመቸ ግቢ ውስጥ አለዚያም የቀን ጭፈራ ቦታዎችን (ፓርቲ ቤቶች) በመጠቀም ልቅ ወሲብ መፈጸም፣ በቡድን እየተከፋፈሉ አምባጓሮና ጸብ መፍጠር፣ አልኮል መጠጥ ወዘተ. ለመምህራንና ለወላጆች የራስ ምታት መሆናቸውን እንሰማለን፡፡ (በተለይ 12ኛ ክፍሎች እንዲያከብሯቸው የሚፈቀዱላቸው (?) ፌስቲቫሎች ለዚህ ዓይነቱ ልቅነት ይበልጡን ምቹ ሆነዋል፡፡

             3 ዕለቱ ሰኞ ነበር፡፡ ከረፋዱ 4 ሰዓት አካባቢ። አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ዋናው ግቢ ቆይቼ ወደ ስቴዲዬም የሚወስደኝን ታክሲ ለመያዝ ወደ መውጫው በር እጣደፋለሁ፡፡ ‹‹በቄንጠኛ ሙድ›› ጸጉሩን ባሳመረ፣ ቁመተኛና አፍንጫ ረጅም ጎረምሳ የሚመሩ ሦስት ሴቶች ከፊቴ ይሄዳሉ፡፡ እየተጓተቱ፣ እየተላፉና እየተሳሳቁ፡፡ ከፊት እየመሩ ወጣን። ወደ ታክሲ ተጠጋን፡፡ አራት ኪሎ የሚል ታክሲ ውስጥ ገባን፡፡ ታክሲው እስኪሞላ የታክሲው ጣሪያ እስኪንቀጠቀጥ የሁካታ ቤት አደረጉት፡፡ የታክሲውን ሒሳብ ሴቶች እንዲከፍሉ ቄንጠኛው ጎረምሳ ተናገረ። የሴቶቹ ቡደን መሪ የመሰለችዋ ተቃወመች፡፡ ‹‹ኧረ እባክህ… ለምነህ ክላስ አስቀጥተኸን ደግሞ ክፈሉ ትለናለህ?›› አፍንጫማው ቀጥሎ የሚጠብቀውን ወጭ እየዘረዘረ ለማሳመን ሞከረ፡፡ ለምን ለምን ሊያወጣ እንደተዘጋጀ በዚህ ጽሁፍ አልገልጸውም። (ፍጹም ጸያፍ ነበር!) የሆኖ ሆኖ ‹‹ሊዝናኑ›› ወደ ቦሌ እየሄዱ ነበር፡፡ የእነዚህን ልጆች ተግባር ስመለከት አንድ ነገር አስታወስኩ፡፡ በ2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የአይሳካ ጉባኤ ላይ ቀረበ ተብሎ አብስትራክቱን ያነበብኩት አንድ ጥናት ነው፡፡ ጥናቱ የተሰራው በዲላ ዩንቨርሲቲ ነው፡፡ በዩንቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በየጢሻው፣ በየጅምር ህንጻው፣ በየኳስ ሜዳው ልቅ መሳሳም ፣ ልቅ ወሲብ ብሎም ውርጃ ብርቅ አይደለም ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ ባለፉት ሁለት ዓመታት (ለአንድ መጽሐፍ ዝግጅት) በአዲስ አበባ ፣ በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በጅጅጋ፣ በባህርዳርና በጎንደር ዩንቨርሲቲዎች ‹‹እንዴት ነው?›› እያለ ጠያይቆ ነበር፡፡ ዩንቨርሲቲዎቹ ብዙ የሚያስደንቁ አጉል ነገሮች ይደረግባቸዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አላማ የተማሪዎቹን አጉል ድርጊት እየዘረዘሩ ማስተዋወቅ አይደለምና እዚሁ ላይ ቢበቃ ይሻላል፡፡ እነዚህ ፊደል ቆጠሩ እየተባሉ በየመስሪያ ቤቱ የሚሰገሰጉ ወገኖች፣ ይህን አጉል ልማዳቸውን ማስቀጠል ስለሚፈልጉ ለሥራ ግድ የሌላቸው፣ ጉቦና ጥቅማጥቅም ፈላጊ ሙሰኞች፣ ሰነፎች፣ ከሀገር ለመሰደድ ቀድመው የሚሰለፉ ተስፋ ቆራጮች፣ ሀገር ለመሸጥ የማያቅማሙ ብኩኖች ይሆናሉ፡፡ አስደናቂው ነገር በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ሆነ በዩንቨርሲቲዎች ውስጥ ያሉ እኒህን አጉል ነገሮች ይተገብራሉ ከሚባሉ ተማሪዎች ከፊሎቹ፣ በትምህርት ውጤታቸው የተሻሉ መሆናቸው ነው። ሌሊቱን በጭፈራ ቤት የምታነጋና በቢራ ግብዣ አለያም በገንዘብ ክፍያ ካገኘችው ባለሃብት ጋር ለመሄድ የማትሰንፍ የዩንቨርሲቲ ተማሪ፤ ሌሊቱን ሙሉ የተማረችውን ስትተነትን መስማት አይገድም። ይህን አስመልክቶ አብዛኛው ሰው እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነገር ይናገራል፡፡ ‹‹ጣጣ የለውም/የላትም!›› በማለት። ጥሩ “ግሬድ” ካመጡ ቢቀብጡስ እንደማለት ነው፡፡ ለመሆኑ ለአንዲት ሀገር የትምህርት ግብ ምንድን ነው? ጥሩ “ግሬድ” ማምጣት የሚችሉ ብኩን ዜጎችን ማፍራት ነው? በዚህ አጉል ህይወት ውስጥ የሚርመሰመሱ ተማሪዎች፤ የተማሩትን ሲያነበንቡልን፣ አውቀው አውቀው ልባቸው ውልቅ ያለ ይመስለናል፡፡ ዳሩ የተሰጠውን ለመስጠት ቴፕሪኮርደርም አቅም አያጣም፡፡ ትምህርት ሰውን መለወጡን የምናውቀው ከተማሪው ደም ጋር ባለው ውህደትና ‹ተማረ› የተባለው ሰው በሚያሳየው ሁለገብ ግብረገብነት እንጅ የማርክስን ቲዎሪ ያነበነበ ሁሉ ተምሯል ማለቱ ይቸግራል፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ተደጋግሞ ተቃውሞን ሲሰማ፣ በጄ ከማለት ይልቅ ለተቃወመው ሁሉ ቅጽል ስም እያስታቀፈ የሚወነጅለው ኢህአዴግ፤ አቅም ወይስ ቅንነት ይሆን ያጣው? ሀገር ይረከባሉ የሚባሉ ወጣቶች እየባከኑ ሲያይ፣ “አሁንም መስመሬ ልክ ነው” ለማለት ያስደፈረው ያለማወቅ ወይስ ያለመፍቀድ አባዜ ይሆን?

           4 በግሌ ወደመንግስት መሥሪያ ቤት ሄጄ ጥሩ መስተንግዶ አግኝቼ አላውቅም፡፡ ሲወለድ በጥሩ ምግባር የተወለደ አጋጥሞን በጥሩ ሁኔታ ቢያስተናግደንም፣ የእሱ የበላይ ወይም የበታች አመናጭቆና አበሳጭቶ ይሸኘናል፡፡ ወጥ የሆነ ስርዓት ለማየት አልታደልንም፡፡ ዳሩ ግን አሁን ልመሰክር የሚገባኝ አንድ እውነት አለ፡፡ ከክልል ክልል፣ ከከተማ ከተማ ስንዘዋወር ባለው ነገር ሁሉ ተስፋ ቆርጠን “ምን ሥርዓት አለ” በምንልበት ሀገር ውስጥ አንጀት የሚያርስ ስርዓት ስናገኝ እንደነቃለን። በሦስት የተራራቁ ዓመታት፣ በሦስት የተለያዩ ከተሞች፣ በሦስት የተለያዩ ግቢዎች ሄጄ፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ፍጹም ድንቅ የሆነ ስርዓት ያየሁት በሀገር መከላከያ ውስጥ ነው፡፡ በግሌ ያጠናሁት ጥናት የለም። የተጠናና ያነበብሁትም እንዲሁ፡፡ ግን እንዲህ ይሰማኛል፡፡ የስራ ሠዓት አቋርጦ ጫት የሚቅም፣ ጉቦ ካልሰጣችሁኝ የሚል ወይም ጸሐይና ዝናብ የሚበግረው፣ አሊያም ወጥቶ ገብቶ አሜሪካን የሚያልም፣ ለአደንዛዥ እጽና ለብልጭልጭ ነገር ሊሸነፍ የፈቀደ ዜጋ፣ ሀገር መከላከያ ውስጥ መኖሩን አልሰማሁም፡፡ በምኒልክ እምነት ዘመናዊ ትምህርትን ማስፋፋት ያስፈለገው ነጻነት፣ ጽናትና ለህዝብ ልብ መታመንን በዜጎች ውስጥ ለማስረፅ ነው፡፡ እነዚህን አንኳር ነጥቦች የኢህአዴግ የትምህርት ስርዓት ሊፈጥራቸው አልቻለም፡፡ በሀገር መከላከያ ውስጥ ግን ያሉ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ ታግሎ የመጣው ኢህአዴግ፤ ጽናትን፣ ነጻነትን እና በህዝብ ልብ መታመንን ገንዘቡ ያደረገ ትውልድ ለማፍራት መከላከያ ላይ ያለውን የማያወላዳ አቋም፤ በዘመናዊ ትምህርቱ ስርዓትም ቢዘረጋ ጥቅምን እንጅ ጉዳትን አያተርፍም፡፡ ያለዚያማ አሁን ባለው አካሄድ ይህችን ሀገር ማን ይረከባታል?



Published in ህብረተሰብ

በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ሰሞኑን በሚጀመረው የ2013 ሴካፋ ላይ ሻምፒዮና አስቀድሞ የዋንጫ ግምት ተሰጥቶት የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በስብስቡ ከ10 በላይ አዳዲስ ተጨዋቾችን በመያዙ ከፉክክር ውጭ የሚሆንበት ሁኔታ ማዘንበሉ ተነገረ።   በሴካፋ ዞን ከሚገኙ 12 ብሄራዊ ቡድኖች በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት  በአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ከፍተኛ ውጤታማነት ያሳየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ስብስብ ለሴካፋ የዋንጫ ድል ተገምቶ ቢቆይም ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው 12 አዳዲስ ተጨዋቾችን በመጥራት የነበሩትንን ትልልቅ ተጨዋቾችን ማሳረፋቸው ከፉክክር ውጭ አድርጎታል፡፡
በዋናው ብሄራዊ ቡድን ስብስብ ሆነው ለ105 ሳምንታት የሰሩት እነ ሳላዲን ሰኢድ፤ ደጉ ደበበ፤ አዳነ ግርማ፤ ሽመልስ በቀለ፤ ጌታነህ ከበደ፤ አዲስ ህንፃ፤ ምንያህል ተሾመ፤ ሶስቱ በረኞች ሌሎች ተጨዋቾች እረፍት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በሴካፋ ቡድናቸው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ እንዳይቋረጥ በሚል ምክንያት ከየክለቡ ከሁለት በታች ተጨዋች መምረጣቸው ግድ ሆኗል፡፡ ዋና አሰልጣኙ  ተተኪ ተጨዋቾችን ለማግኘት እና ጎን ለጎን ለቻን ውድድር ለመዘጋጀት በማቀዳቸው ለሴካፋው በመረጡት ቡድን አዳዲስ ተጨዋቾችን ለማብዛት እንደወሰኑ ተገልጿል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ ወደ አህጉራዊ ውድድር በመግባት በደቡብ አፍሪካ በተዘጋጀው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፍ፣ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከአፍሪካ ምርጥ አሥር ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ በመሆንና በደቡብ አፍሪካ በሚደረገው 3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ውድድር ተሳታፊነቱ  በምሥራቅ አፍሪካ እግር ኳስ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩ ተወስቶለታል፡፡  በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፉት 29 ወራት ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ 10 ጨዋታዎችን ሲያደርግ 5 ጨዋታዎች አሸንፎ፤ በ2 ጨዋታ አቻ ተለያይቶ፤ በ3 ጨዋታ ተሸንፏል፡፡ በእነዚህ ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቹ ላይ 14 ጎሎች አግብቶ 10 እንደተቆጠረበት ይታወሳል፡፡
የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ)የእግር ኳስ ሻምፒዮና 18 እስከ ታኅሣሥ 2 በኬንያ ሦስት ከተሞች ናይሮቢ፣ ሞምባሳና ማቻኮስ ሲካሄድ፤ የፊታችን ረቡዕ በናይሮቢ ከተማ በሚገኘው የናያዮ ስታድዬም በመክፈቻው ግጥሚያ  ኢትዮጵያ ከኬንያ ይገናኛሉ፡፡
12 ብሄራዊ ቡድኖች በሶስት ምድብ የተደለደሉ ሲሆን ብቸኛዋ ተጋባዥ አገር የደቡብ አፍሪካዋ ተወካይ ዛምቢያ ናት፡፡ በምድብ 1 ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ዛንዚባርና ሱዳን፤ በምድብ 2 ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ብሩንዲ እና ሶማሊያ እንዲሁም በምድብ 3 ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳንና ኤርትራ መደልደላቸው ይታወቃል፡፡  
በወጣው የውድድር መርሃ ግብር መሰረት በምድብ 1 የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ረቡዕ ከአዘጋጇ ኬንያ ጋር ከሚያደርገው የመክፈቻ ግጥሚያ በኋላ ሁለተኛ ጨዋታውን የዛሬ ሳምንት ከዛንዚባር አድርጎ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ከ3 ቀናት በኋላ ከደቡብ ሱዳን ጋር እንደሚገናኝ ይጠበቃል፡፡
በሴካፋ ዞናዊ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ  በ17 የውድድር ዘመናት የተሳትፎ ታሪኳ ለአራት ጊዜያት በ1987፤ በ2001፤ በ2004 እና በ2005 እኤአ ላይ  ሻምፒዮን መሆኗ ሲታወቅ አንድ ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን ለሁለት ጊዜያት ደግሞ አራተኛ ደረጃን በማስመዝገብ በምንጊዜም ውጤታማነት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ነች፡፡
 13 ጊዜ የውድድሩ ሻምፒዮን በመሆን ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው ኡጋንዳ ስትሆን ኬንያ 5 ጊዜ ሻምፒዮን፤ 7 ጊዜ ሁለተኛ፤ 6 ጊዜ ሶስተኛ እንዲሁም አራት ጊዜ አራተኛ ደረጃን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ታንዛኒያ፤ ማላዊና ሱዳን በውድድሩ እኩል ሶስት ሶስት ጊዜ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡
ውድድሩ ባለፈው ዓመት በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ውስጥ ሲካሄድ ኢስታር አፍሪካ ብሬዌሪስ በታስከር ብራንዱ በ450ሺ ዶላር ስፖንሰር ተደርጎ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ሱፕር ስፖርት፤ ኮካ ኮላ እና ጎ ቲቪ አዲሶቹ የሴካፋ ስፖንሰሮች ናቸው፡፡

ከስምንት ወር በኋላ በብራዚል አስተናጋጅነት በሚጀመረው 20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት 32 ብሄራዊ ቡድኖች ከ29 ወራት የማጣርያ ውድድሮች በኋላ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ  ታውቀዋል፡፡  
በዓለም ዋንጫው ለመሳተፍ በዓለም ዙርያ ከሚገኙ 6 ኮንፌደሬሽኖች የተውጣጡ 203 አገራት መካከል በተለያዩ የማጣርያ ምእራፎች ሲደረግ የቆየው ፉክክር ከ29  ወራት በኋላ ያበቃ ሲሆን 816 ግጥሚያዎች ተደርገው 2334 ጎሎች ከመረብ አርፈዋል፡፡
አዘጋጇ ብራዚል ለ20ኛ ጊዜ፤ጀርመንና ጣሊያን ለ18ኛ ጊዜ፤ አርጀንቲና ለ16ኛ ጊዜ፤ ሜክሲኮ ለ15ኛ ጊዜ፤ ስፔን፣እንግሊዝና ፈረንሳይ ለ14ኛ ጊዜ፤ ቤልጅዬም ለ12ኛ ጊዜ፤ ሆላንድ ፣ አሜሪካ፣ ስዊዘርላንድና ራሽያ ለ10ኛ  ጊዜ፤  ቺሊና ደቡብ ኮርያ ለ9ኛ ጊዜ፤  ካሜሮን ለ7ኛ ጊዜ፤ ፖርቱጋል ለ6ኛ ጊዜ፤ ኮሎምቢያ ጃፓን፣ ናይጄርያ ለ5ኛ ጊዜ፤ አውስትራሊያ፣ ክሮሽያ፣ኢራን፣ ኮስታሪካና አልጄርያ ለ4ኛ ጊዜ፤ አይቬሪኮስት፣ ጋና፣  ግሪክ፣ ሆንዱራስና ኢኳዶር ለ3ኛ ጊዜ  የዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸውን ሲያገኙ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የምትሳተፈው  ቦስኒያ ሄርዞጎቪና ብቻ ናት፡፡ የምድብ ድልድሉ ከ13 ቀናት በኋላ በብራዚሏ ከተማ  ባህያ የሚወጣ ሲሆን ስምንቱ የቡድን አባቶች አዘጋጇ ብራዚል፤ስፔን፤ ጀርመን፤ አርጀንቲና፤ ኮሎምቢያ፤ ቤልጅዬም፤ ስዊዘርላንድ እና ኡራጋይ  እንደሆኑ ታውቋል፡፡
20ኛው ዓለም ዋንጫ በ32ቱ ብሄራዊ ቡድኖች ተመጣጣኝ ብቃት፤ በምርጥ ተጨዋቾች መብዛት፤ በከፍተኛ የተመልካች ትኩረት ምርጥ እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡  በተለይ ውድድድሩን ለማስተናገድ በብራዚል 12 ትልልቅ ከተሞች የሚገኙትና እስከ 668 ሺ ተመልካቾች በድምሩ ማስተናገድ የሚችሉት 12 ስታድዬሞች በአገሪቱ ህዝብ እግር ኳስ አፍቃሪነት ማራኪ ድምቀት እንደሚኖራቸው ተጠብቋል፡፡ ዓለም ዋንጫውን በብራዚል ተገኝቶ ለመከታተል የሚፈልግ አንድ ስፖርት አፍቃሪ ለ13 ቀናት ቆይታው ከ150ሺ እሰከ 200ሺ ብር ወጭ እንደሚያስፈልገው ተሰልቷል፡፡ በስታድዬም መግቢያ ትኬት ሽያጩ አስደናቂ ትኩረት ላገኘው ውድድሩ 6.15 ሚሊዮን የትኬት ግዢ ማመልከቻዎች እንደቀረቡበት  የገለፀው ፊፋ 70 በመቶውን ብራዚላውያን ሸፍነውታል ብሏል፡፡ የውድድሩ አዘጋጆች በመጀመርያ ዙር ሽያጭ 889305 ትኬቶችን ለገበያ አቅርበው ብራዚል 71.5 በመቶውን በመሸፈን 625 276 ትኬቶችን ገዝታለች፡፡ አሜሪካና እንግሊዝ 66646 እና 22257 ትኬቶችን እንደቅደምተከተላቸው በማግኘት ውድድሩን ለመታደም ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው ተመልክቷል፡፡
20ኛው ዓለም ዋንጫ በርካታ የዓለማችን ምርጥ ተጨዋቾች አምልጧቸዋል፡፡ ከእነሱም መካከል የስዊድኑ ዝላታን ኢብራሞቪች፤ የቼከ ቶማስ ሮስዝስኪ፤ የኦስትርያው ዴቪድ አላባ፤ የሮማንያው አድርያን ሙቱ፤ የሴኔጋሉ ፓፓ ሲሴ፤ የግብፁ መሃመድ አቡትሪካ፤ የቶጎው ኢማኑዌል አደባዬር ይጠቀሳሉ፡፡

እኛ ተርፈናል፤ እዛ ላሉት ድረሱላቸው
ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተገደው እየተደፈሩ ነው
እስር ቤት አንዲት ነፍሰ ጡር ሞታብናለች - የስደት ተመላሾች  

ሳኡዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ ወደ አገሯ የገቡ ስደተኞችን በሃይል ማስወጣት ከጀመረች ሁለተኛ ሳምንቷን ያስቆጠረች ሲሆን ህገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደአገራቸው የመመለስ ዘመቻው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ዜጐችን ከሳኡዲ ለማምጣት ባለፈው ሳምንት በቀን ሰባት በረራዎች ይደረጉ እንደነበር ያስታወሱት የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በዚህኛው ሳምንት በቀን 12 በረራዎች እየተደረጉ ዜጐችን ማምጣቱ እንደቀጠለና እስከትላንት ድረስ ከ19ሺ በላይ ዜጐች መመለሳቸውን ገልፀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በቦሌ አየር ማረፍያ ተገኝተው ተመላሾቹን ያነጋገሩ ሲሆን፤ ስደተኞቹን ለማቋቋም ከክልል መንግስታት ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ሁለት ሌሎች ቦታዎች ለስደተኞቹ በጊዜያዊ መጠለያነት እያገለገሉ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ከሶስት የሳኡዲ ተመላሾቹ ጋር ባደረገችው ቆይታ የስደት መከራቸውን እንደሚከተለው ነግረዋታል፡፡

“ኤምባሲያችን አይሰማም እንጂ ደጋግመን ነግረናል”
ራውዳ ጀማል ትባላለች፡፡ የሃያ ዓመት ወጣት ናት፡፡ ስለራስዋም ሆነ በሳኡዲ ስላሉ ኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ሁኔታ ስታወራ እያለቀሰችና እየተወራጨች ነው፡፡ ለማነጋገር ስቀርባት “ወንድ ከሆናችሁ ጋዜጠኞች ነን፣ የህዝብ አፍ ነን ካላችሁ፤ እዚህ ተቀምጣችሁ፣ “ሁለት ሰው ሞተ” እያላችሁ ከምታቅራሩ ሳኡዲ ሂዱና በየቀኑ ሁለት ሶስት ሰው የሚሞትበትን እልቂት ተመልከቱ፣ “ሰዎቹን ምን እየሰራችሁ ነው?” ብላችሁም ጠይቁልን” አለችኝ። መቅረፀ ድምፄን ሶስት አራት ጊዜ ያስጠፋችኝ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ለቃለ ምልልስ ፈቃደኛ ሆነችልኝ፡፡
ስንት ዓመት ቆይተሽ መምጣትሽ ነው?
ከሁለት ዓመት በኋላ ነው የመጣሁት፡፡ እስከ አስረኛ ክፍል የተማርኩት አዲስ አበባ ቢሆንም፤  የኮምቦልቻ ልጅ ነኝ፡፡
እንዴት ነበር የሄድሽው?
በፓስፖርት… በኮንትራት ነበር የሄድኩት … ካላስ! የሰውየው ልጆች ግን “የማይሆን” ፊልም ተመልከቺ እያሉ ያስቸግሩኝ ነበር፡፡ ሲመረኝ ጠፍቼ ወጣሁ፡፡ ከዚያም ከጓደኞቼ ጋር በነፃነት ቤት ተከራይተን እየኖርን፣ በ1800 ሪያል ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ቤተሰቤንም ገንዘብ እየላኩ እረዳ ነበር፡፡
ወደ አገርሽ እንዴት ተመለስሽ?
ውጡ ሲባል… ረብሻ ሲነሳ.. ጓደኞቻችን ሲሞቱ.. ሲደፈሩብን.. ‘ድሮም ስደተኛ ክብር የለውም’ ብዬ ተመልሼ መጣሁ..ከሚገሉኝ ከሚያበለሻሹኝ ብዬ እጄን ሰጠሁ፡፡ ብዙ ኢትዮጵውያኖች ችግር ላይ ናቸው.. እባካችሁ ድረሱላቸው፡፡ ብርዱም ፀሃዩም ሲፈራረቅባቸው.. ያሳዝናሉ፡፡ ብዙ ያልመጡ አሉ፤ መምጣት እየፈለጉ፡፡ ስቃይ ላይ ናቸው፡፡ እኔ አሁን አስራ ሶስት ቀን ታስሬ ነው የመጣሁት፡፡
እስቲ ስለ እስሩ ንገሪኝ …
ሁለት ቀን ያለ ምግብ ያለ ውሃ ነው የታሰርነው። ከዛ በኋላ ግን ጥሩ ምግብ ሰጥተውናል፣ ጥሩ መኝታም አግኝተናል፡፡ ብዙዎቹ ግን ከእኛ የባሰ ችግር ላይ ናቸው፡፡ መጠለያ ያላገኙ አሉ…ኤምባሲያችንም አይሰማም እንጂ ስንት ጊዜ ደውለን ተናግረናል መሰለሽ፡፡ ግን የሚሰማ የለም፡፡  
ከአገራችን ውጡ ካሉ በኋላ ትዕግስት ያጡና መልሰው ይዩዙናል፡፡ በዛን ጊዜ አበሻው፣ ሻንዛ/ጩቤ ይመዛል፡፡ ፖሊስ ራሱን ለማዳን ይተኩሳል። እኔ እንደውም ደህና ነኝ፤ እዛ ላሉት ድረሱላቸው። በምድረ ዱርዬ እየተደፈሩ ነው ያሉት /ለቅሶ/ ስንት ህፃናት አሉ የሚሞቱ፣ የሚታመሙ፡፡ ስንመጣ ደሞ፤ ሻንጣ  አትያዙ ተብለን ተመናጭቀን…በጥፊ ተመትተን..መከራችንን በልተናል፡፡
ወንዶችና ሴቶች ለብቻ ነበር የተቀመጣችሁት?
የተቀመጣችሁት አትበይ! የታሰራችሁት በይ፡፡ … የሴት እስር ቤት ለብቻው ነው በሴቶችና በህፃናት ለቅሶ የተሞላ ነው፡፡ እኔ ራሴ ስድስት ያበዱ ሴቶችን ይዤ መጥቻለሁ…/ለቅሶ/
አሁን ቤተሰብ እየጠበቅሽ ነው?
ነበረ ግን ሻንጣዬ ጠፋብኝ፡፡ በርግጥ ጤነኛ ሆኖ መምጣትም ቀላል አይደለም፡፡ እዛ ያሉትን ጥለናቸው ስንመጣ እያለቀስን ነው፡፡ እስር ቤቱ ውስጥ አንድ እርጉዝ ሞታብናለች፡፡ እዛው እስር ቤት እያለን ምጥዋ መጣ፤ ግን የህክምና እርዳታ ባለማግኘትዋ ሞተች፡፡
እስር ቤት ያሉት ምን ያህል ይሆናሉ?
ሰማኒያ ክፍል አለ..በየክፍሉ ስልሳ አምስት ስልሳ አምስት ሰው ነው ያለው፡፡ መካሲመሺ እስር ቤት ይባላል፡፡ የወንድና የሴት እስር ቤት የተራራቀ ነው፡፡ በጣም ረጅም ከመሆኑ የተነሳ በመኪና እንጂ በእግር  አይሞከርም፡፡ በአሁኑ ሰዓት በከተማው ያለው እስር ቤት ሞልቶ የመዝናኛና የስብሰባ አዳራሹን ሁሉ እስር ቤት አድርገውታል፡፡ የተደፈሩት የሞቱት..ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንዷን እርጉዝ ለሶስት ሲደፍሯት ሞታለች፡፡
የሌሎች አገር ስደተኞችም እየወጡ ነው ተብሏል…
አዎ፡፡ ኢትዮጵያዊው ከበደሉ ብዛት የተነሳ እየተናነቀው እኮ ነው ግጭቱ የሚከረው፡፡ ሚስቱንኧ እህቱን ከእጁ መንትፈው ሊወስዱበት ሲሉ ነው ጦርነት የሚነሳው፡፡ አበሻ ወንድ እየሞተ ያለው ‹‹ሴቶቻችንን አትንኩብን..›› ስለሚል እኮ ነው፡፡ ኤምባሲው ሊደርስላቸው ይገባል፡፡

“የሁለት ሰው መርዶ ይዤ መጥቻለሁ”
ስምሽ ማን ነው?
ፀጋ ኪዳኔ ገብረኪዳን
ምን እየጠበቅሽ ነው?
ዘመድ አለችኝ አዲስ አበባ የምትኖር፤ እስዋ እስክትመጣ እየጠበቅሁ ነው፡፡
ሳኡዲ ምን ያህል ጊዜ ቆየሽ?
ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ነው ከሪያድ/ሞንፋ የመጣሁት፡፡ ከኢትዮጵያ ስሄድ በኮንትራት ቢሆንም በባህር ከሄዱት ስደተኞች የተለየ ክብር አላገኘሁም፡፡ ጭቅጭቅ፣ ስድብና ድብደባ  ሲበዛብኝ ከተቀጠርኩበት ቤት በስምንተኛ ወሬ ወጥቼ ጠፋሁ፡፡ የሄድኩት ለአንድ ስራ ብቻ ተዋውዬ ነበር። የምተኛው ግን ከሁለት ሰዓት አይበልጥም ነበር፡፡ ሥራ ብቻ ነው 24 ሰዓት!
እስቲ ስለደረሰብሽ ችግር በዝርዝር ንገሪኝ..
በ700 ሪያድ ተቀጥሬ ነበር ከዚህ የሄድኩት፡፡ አሰሪዬ ቤት አራት ትላልቅ ወንድ ልጆች አሉዋት። የእህትዋ ልጆችም እዚያው ነው የሚኖሩት፡፡ ‹‹ወሲብ ካልፈፀምን..›› ብለው ያስቸግራሉ፡፡ በጣም ተሰቃየሁ፡፡ ከአቅሜ በላይ … ለህይወቴ በጣም አስፈሪ….ሲሆንብኝ ወጣሁ፡፡
ከአቅሜ በላይ ስትይ …
ልጆቹ ወሲብ ካልፈፀምን ብለው አሻፈረኝ ስላቸው፣ “በቢላ እናርድሻለን” እያሉ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡ እምነቴን እንድቀይር ሁሉ ይፈልጋሉ። አፈር ድሜ በላሁ፡፡ ሰርቼ ለፍቼ … በዚያ ላይ ነፃነት አልነበረኝም፡፡ ወገቤ፣ ዓይኔ ታመመ፡፡ እነሱ እኮ ሃያ አራት ሰዓት እየበሉ እየጠጡ ነው፡፡ በዚያ ላይ በእጅሽ ላይ ስልክ ማየት አይፈልጉም፡፡ ሁሉ ነገር ሲያንገፈግፈኝ ሁለት ወር የሰራሁበትን ገንዘብ ጥዬ ወጣሁ፡፡ ከዛ ኤጀንሲው ለሌላ ሰው ሸጠኝ፤ በአስር ሺህ ሪያድ፡፡ እዚያም ግን  አልተመቸኝም። ስራው ሃያ አራት ሰዓት ነበር፡፡ አምስት ሰው እንኳን የማይችለው ስራ ነበር፡፡ አንድ ኩንታል ሊጥ አብኩቼ፣ ለሱቅ የሚሸጡት ብስኩት ጠብሼ፣ ሰባት መቶ ሪያል ነበር የሚከፈለኝ፡፡ ሁለት ወር ሙሉ እንደምንም ድምጼን አጥፍቼ ሰራሁ… በእንቅልፍ እጦት ልወድቅ እየተንገታገትኩ፡፡ እፊታቸው ላይ ግን ደስተኛ እመስል ነበር፡፡ ሰውነቴ እየመነመነ መጣ፡፡ ይሄኔ ድጋሚ ለመጥፋት ተዘጋጀሁ፡፡
“ለሌላ ሰው ሸጠኝ” ያልሽው … ኢትዮጵያዊ ነው?
/እንባዋ እየፈሰሰ/አረብ ነው፡፡ ወደ ሳኡዲ ከላከኝ ኤጄንሲ ጋር አብሮ ይሰራል፡፡ የረመዳን ጊዜ ደግሞ ሱቃቸው ወሰዱኝ፤ የአንድ ሰዓት መንገድ ተጉዞ ሌላ ቤት አላቸው፡፡ እዛ ይዘውኝ ሲሄዱ  ስራ ይቀልልኛል ብዬ ነበር፡፡ … ግን የባሰ ሆነብኝ፡፡ ለካ ጓደኞቻችን ወደው አይደለም ራሳቸውን የሚያጠፉት፤ አብደው ጨርቃቸውን ጥለው በየጎዳውና የወጡትና መንገዱ የወደቁት ... የወገብና የአእምሮ በሽተኞች የሆኑት? “ምነው እናቴ ስትወልጅኝ በመሃፀንሽ ውስጥ ደም ሆኜ በቀረሁ? እናቴ እባክሽ መልሰሽ ዋጪኝ” አልኩኝ፡፡ ራሴንና ቤተሰቤን ልረዳ ስንገታገት ከፊታቸው ድፍት ብል እኮ … እንደሰው ከቆጠሩኝ ... ሬሳዬን ለእናቴ ይልኩላት ይሆናል፡፡ ያለዚያ ግን የሀገራቸው መንግስት አውጥቶ ይቀብረኛል፡፡
ከዚያ ሁሉ በፊት ጠፍቼ መውጣት እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ አንድ ቀን ረመዳን ካፈጠሩ በኋላ ቤተሰቡ ተሰብስቦ ሊዝናኑ ወጡ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ቶሎ ብዬ የሴትየዋን ሙሉ ልብስ ለብሼ፣ ሽፍንፍን ብዬ ወጣሁ፡፡
ሻንጣ ምናምን ሳትይዢ?
ባዶ እጄን ነው የወጣሁት፡፡ የሰራሁበት ገንዘብ እንኳን በእጄ የለም፡፡ በቃ ዝም ብዬ ወጣሁ፡፡ ፓኪስታናዊ የታክሲ ሾፌር አገኘሁ፡፡ ‹‹ምን ሆንሽ?›› ብሎ ሲጠይቀኝ በዝርዝር ነገርኩት፤ አዘነ፡፡ ‹‹ሪያድ የሀበሻ ሃገር ነው፤ ብዙ ኢትዮጵያዊ አለ›› ብሎ እዛ (በነፃ) ወሰደኝ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን አገኘሁ፡፡
እዚያ መኖር ጀመርሽ ማለት ነው?
ሳያቸው በጣም ነው ያለቀስኩት፡፡ አገሬ የገባሁ ይመስል..መሬት ሁሉ ስሚያለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ በባህር (በህገወጥ መንገድ) የመጡ ሴቶች ነበሩ። ከእነሱ ጋር አንድ ቤት በስድስት መቶ ሪያድ ለስድስት ወር ተከራይተን አብረን እየኖርን እንሰራ ጀመር፡፡
ቤቱን ለስንት ተከራያችሁ?
አስር ነበርን፡፡ ሁለት ወር እንደሰራሁ ግን በአካባቢው ግጭት ተነሳ፡፡ እግሬ አውጪኝ ብለን በየፊናችን ተበታተንን፡፡
ምን ዓይነት ግጭት?
መንግስት የሌለበት አገር ይመስል ጐረምሶች በር እያንኳኩ በሽጉጥ፣ በካራ፣ ሰው መግደል ጀመሩ፡፡ ስለዚህ ‹‹እጃችንን እንስጥ›› ብለን ተማከርን፡፡ ሌላው ችግር ፖሊስ፤ ትዳር መስርተው የሚኖሩትን የአበሻ ወንዶች እየወሰደ፣ ሴቶችን ለብቻቸው ይተዋቸው ነበር፡፡ በቤቱ ወንድ አለመኖሩን የተገነዘበ የአገሩ ዱርዬዎች (እንኳን ለአበሻው ለመንግስትም ልባቸው ያበጠ ነው) ሴትዋን ለአራትና ለአምስት እየሆኑ መድፈር ያዙ፡፡ ከእኛ ጎን የነበሩትን ሲያሰቃይዋቸው አይተናል፡፡ ወንዶቹን ፖሊስ ሲወስዳቸው ጎረምሶቹ ተከትለው ይገቡና ሴቶቹን መጫወቻ ያደርጓቸዋል/ለቅሶ/፡፡ አንድ ያየሁትን ልንገርሽ../ረጅም ትንፋሽ/እነዚህ ጐረምሶች…ሶስት ሴቶች ያሉበት ክፍል ውስጥ ገብተው ለሰባት ደፈሯቸው፡፡ /ማውራት አልቻለችም፤ ሳግና እንባዋ እያቋረጣት/..ከሶስቱ አንዷ የሰባት ወር ነፍሰጡር ነበረች፤ ሲገናኝዋት ሞተች፡፡ አንዷን ደግሞ ለሰባት ደፈሯትና ገድለው ጥለዋት ሊወጡ ሲሉ ሽርጣ/ፖሊስ መጣ፡፡ ከፖሊስ ጋር ተኩስ ገጥመው እርስ በርስ ተገዳደሉ፡፡ የሀበሻ ወንድ ከእህቱ ወይንም ከሚስቱ ሊለዩት ሲመጡ አልለይም ይልና ይገደላል፤ ይደበደባል … በቃ እልቂት ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ ብለሽ ካራ ቆሬ እንደምትይው..ሪያድ ብለሽ ሞንፋ የሚባል አካባቢ በርካታ አበሾች ይኖራሉ፡፡ እኔ እንኳን የማውቀው … ከአምስት በላይ ሴቶች እንደተገደሉ ነው፡፡  መላ አካላቸውን ቆራርጠው ነው የጣሏቸው፡፡ ግን ይሄ ሁሉ መከራ ምን አድርገን ነው?
አንቺ እንዴት መጣሽ ወደ አገርሽ?
እጄን ሰጠኋ፡፡ አሰሪዬ ‹‹የት ልትሄጂ ነው?›› ብላ ስትጠይቀኝ፡፡ ‹‹አንድ ጓደኛዬ ልትወልድ ነውና ልጠይቃት ..›› ብዬ የሰራሁበትንም ሳልቀበል ወጣሁ፡፡ ምክንያቱም ብትገለኝስ ብዬ ፈራሁ፡፡ አብዛኛው አበሻ ከስራ ወደቤቱ ሲሄድ እየተያዘ ነው የሚመጣው፡፡ የሰራበትን የለፋበትን ሳይዝ ባዶ እጁን፡፡ እና እኛም ነገሩ ስላስፈራን እጃችንን ሰጠን። በቃ እኔም ወደ እዚህ መጣሁ፡፡
ዛሬ ላይ ሆነሽ ስታስቢው ወደዛ በመሄድሽ ምን ይሰማሻል?
መጀመሪያ ከዚህ ስሄድ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር፤ የራሴንና የቤተሰቤን ህይወት ላሻሽል እንደሆነ ተስፋ በማድረግ፡፡ ከዛ በኋላ ግን  ከስራው ብዛት የተነሳ ከጥቅም ውጪ ልሆን ነው ብዬ እጅግ አምርሬ አለቅስ ነበር፡፡ በጣም ስጋት ያዘኝ፡፡ ግን ከሞት ተርፌ ወደዚህ ስመጣ አምላኬን አመሰገንኩ፡፡
ቤተሰብሽ መምጣትሽን አውቀዋል?
አላወቁም፡፡ ምን እያሰቡ ይሆን? ይሄን ሁሉ ነገር እየሰሙ፡፡ እናቴ መንገድ መንገድ እያየች ይሆናል፡፡ ደሞ ከእኛ አካባቢ ልጆች ብዙ የሞቱ አሉ፡፡..አሁን እኔ ራሴ የሁለት ሰው መርዶ ይዤ መጥቻለሁ፡፡ እናቴም ሰው ሲመጣ ‹‹ልጄን አይታችኋል?›› ትል ይሆናል፡፡ እኔስ መጣሁ..በረሃ ላይ ተደፍተው ለመምጣት ወረፋ እየተጠባበቁ ያሉ ህጻናትና ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ እዚህ የመጣነው እኮ ግማሽ አንሞላም፡፡ በሳኡዲ የኢትዮጵያውያን እንባ ያሳዝንሻል፡፡ ብዙዎቹ በሃዘን ላይ ናቸው፤ ድረሱላቸው፡፡


“ሰባት ያበዱ ሴቶችን አይቻለሁ”

ስምሽን ንገሪኝ..?
ሀያት አህመድ
እስቲ አካሄድሽን ንገሪኝ …
ከደሴ ነው በኤጀንሲ የሄድኩት፡፡ የምሰራው በጠለብ/በህጋዊ መንገድ ነበር፡፡ ሰዎቹ ሳይመቹኝ ሲቀሩ..ብዙ ጓደኞቻችን ችግር ሲደርስባቸው ሳይ፣ ስልካችንን ቀምተው ቤተሰቦቻችን በሃሳብ ሲያልቁ፣ እኔም ነገሩ ስላልተመቸኝ ጥዬ ጠፋሁ፡፡ ከዛም በሃጂና ኡምራ የሄድኩ አስመስዬ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ፡፡
በጠለብ ስንት ጊዜ ሰራሽ?
ሶስት ወር ነው የሰራሁት፡፡
አሰሪዎችስ ቤት የሚደርስብሽ ችግር ምን ነበር?
በቤት ውስጥ ያሉ ወንዶች ያስቸግሩኝ ነበር፤ አስገድዶ ለመድፈር ይተናነቁኛል፡፡ አሰሪዬ በስራዬ  አትደሰትም፣ ያጠብኩትን ነገር እንደገና እጠቢ ትለኛለች፡፡
“የኢትዮጵያ ሰራተኞች ሞያ የላቸውም፣ “ሞዴስ እንኳን በአግባቡ መጠቀም አይችሉም፣ በዚያ ላይ ወንዶቻችንን ያባልጋሉ” የሚል ክስ ከሳኡዲ ሴቶች ይሰማል፡፡ አንቺ ምን ትያለሽ?
በጭራሽ! እኛ ደልቶን ይሄን ልናስብ? አንገታችንን ቀና አድርገን እንኳን ለመሄድ እንቸገራለን እኮ፡፡ እዛ ቦታ ላይ እኛን ብታይ ኢትዮጵያዊነት ያስጠላሻል፡፡ አለባበሳችን ምንድን ነው፣ ሁኔታችንስ፣ ኑሮዋችንስ..እኛ የእነሱን ባል የምናባልግ ምን አምሮብን፣ እንዴት ሆነን ነው?  እኛን እኮ ይጠየፉናል፡፡ በምን አንገታችን ቀና ብለን ነው የእነሱን ወንዶች የምናባልገው? እኛ እኮ ለህይወታችን እየሰጋን ነው… እያንዳንዷን ቀን የምናሳልፈው፡፡ በርግጥ የገጠር ልጆችም ይሄዳሉ። እንግዲህ በንፅህና የሚታሙት እነሱ ናቸው፡፡ ግን ስንቱን አእምሮውን አሳጡት…. ወይኔ!!..አሁን ስንመጣ እንኳን ጅዳ ኤርፖርት ውስጥ ሰባት ያበዱ ልጆችን አይቻለሁ፡፡ ‹‹ይዛችኋቸው ሂዱ›› ሲሉን ነበር፤ እንዴት አድርገን እንይዛቸዋለን? ጥለናቸው ነው የመጣን፡፡ አይ ዜጎቻችን! እየቀወሱ፣ እየተደፈሩ፣ እየተደበደቡ፣ እየተጣሉ ነው ሜዳ ላይ ….ተመልካች አጥተው፡፡
ጣትሽ ላይ የጋብቻ ቀለበት አያለሁ … ባለትዳር ነሽ?
ፈትቻለሁ፡፡ የአስር ዓመትና የስምንት ዓመት ልጆች አሉኝ፡፡ እነሱን ላሳድግ ብዬ ነው በሰው አገር የተንገላታሁት፡፡ ገንዘብ እልክ ነበር፡፡ ሆኖም እኔም አልተለወጥኩም፤ ለልጆቼም አልሞላልኝም፡፡ አንድ ጊዜ ሆድ ብሶኝ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር፡፡ ታውቂያለሽ… ልጆቼ በዓይን በዓይኔ መጡብኝና … ከድርጊቴ ታቀብኩ፡፡
አይኔ እንቅልፍ ካጣ ስንት ጊዜው ሆነ መሰለሽ… አይኔ ስር ጥቁር ብሎ የምታይው፣ የበለዘ የሚመስለው እኮ በእንቅልፍ እጦት የተፈጠረብኝ ነው፡፡ ጀርባዬን ያመኛል፡፡ ብዙ ሰዓት የምቆምበት እግሬንም እጅግ ታምሚያለሁ፡፡ አሁን ለትንሽ ጊዜ  ማገገም አለብኝ፡፡
ጂዳ ኤርፖርት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የሚጠባበቁ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሉ ይባላል…?
በጣም ብዙ እንጂ! ‘ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገር ነቅሎ ነው እንዴ የወጣው ብዬ ተደንቄያለሁ፡፡ በጣም ያዘንኩት ግን ወደዚህ ስመጣ ኤርፖርት ሰባት ያበዱ ልጆች ስመለከት ነው፡፡ እዛ ያለው ኤምባሲያችን እንዴት  ወደ አገራቸው አይመልሳቸውም? ‹‹እህ›› ብሎ ችግራቸውን የሚያደምጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ እስቲ አስቢው…ሰባት ሴቶች አብደው አይቻለሁ፤ በአይኔ በብረቱ፡፡ አንዷ ልጅዋ ሞታባት (በረሃብ ነው) የቀወሰችው፡፡ ስድስቱ ደግሞ በስራ ቦታቸው ቀውሰው፣ አሰሪዎቻቸው ናቸው አምጥተው የጣልዋቸው፡፡ የምናየው ነገር ሁሉ ለዓይን ይዘገንናል፡፡
ከዕረፍት በኋላ ምን  ልትሰሪ አቀድሽ…?
አሁን ጤንነት አይሰማኝም፤ ካገገምኩ በኋላ እንግዲህ … እንጃ ምን እንደምሰራ፡፡ አንድ ዓመት ከሶስት ወር ተቀምጬ ነው የመጣሁት፡፡ ከአስርና አስራ አምስት ዓመት በላይ የኖሩትም ‹‹ምንድነው የምንሰራው..›› የሚል ነው ጥያቄያቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ኖረው ቢመጡም ምንም የያዙት ነገር የላቸውም፡፡ በጣም ያሳሰበኝ እሱ ነው፡፡
ከአሁን በኋላ ወደ ሳኡዲ የመመለስ ሃሳብ አለሽ?
አላህ ያውቃል፡፡    

ኢህአዴግም ያልተሰደደው ሥልጣን ላይ ስለሆነ ነው!
የደከመው ባለስልጣን ማረፍ እንጂ አምባሳደር መሆን የለበትም!

በአሁኑ ጊዜ የቱንም ያህል “ልማታዊ” ለመሆን ቢሞክሩ ፈፅሞ ያልተሳካላቸው የመንግስት ተቋማት ቢኖሩ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽንና ኢትዮ ቴሌኮም ናቸው፡፡ (ልማታዊ ያልሆነ ሁሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነው ማለት ግን አይደለም!) መብራት ሃይል መብራት እምቢ ሲለው፣ ቴሌኮምም ኔትዎርክ (በቴክኖሎጂ ግንኙነትን ማቀላጠፍ) አልሆንልህ ብሎታል (ምኑን ኖሩት ታዲያ?!)
የኢትዮ ቴሌኮም ሃላፊዎች ሰሞኑን ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ በሰጡት ማብራሪያ፤ የኔትዎርክ መቆራረጥ የሚከሰተው በሃይል መቆራረጥና በኦፕቲክ ፋይበር መቆራረጥ እንደሆነ ገልፀዋል (በመቆራረጥ አለቁ እኮ!) ቴሌኮም እስካሁን የስራ አጋሩ በነበረው መብራት ኃይል ላይ የጣለው እምነት ተሸርሽሮ ማለቁን የሚጠቁም ፍንጭ እንደታየ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በሰሞኑ ማብራሪያው በኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ የሚፈጠረውን የኔትዎርክ መቆራረጥ ችግር ለመቅረፍ ጄነሬተር እጠቀማለሁ ብሏል - ቴሌኮም፡፡ (እቺን ለማሰብ ግን ይሄን ሁሉ ጊዜ!) ይሄ ሁሉ የኔትዎርክ መቆራረጥና የኢንተርኔት አገልግሎት መንቀራፈፍ ቢኖርም ግን “የደንበኞቼን ቁጥር 26 ሚሊዮን አድርሻለሁ” ብሎናል - ቴሌኮም፡፡ (“የኔትዎርክ መቆራረጥ የደንበኞች መቆራረጥን አላስከተለብኝም” እያለ ነው!) እኔ ግን … ቴሌኮምን ብሆን አፌን ሞልቼ “ደንበኞቼ” አልልም ነበር፡፡ (አገልግሎት ሳይኖር ደንበኛ?) እናም … ደንበኞቼ ሳይሆን “የክብር ደንበኞቼ” ነበር የምላቸው፡፡ ለምን መሰላችሁ … እኒህ ሁሉ “ደንበኞች” እኮ በኔትዎርክ መቆራረጥ ሳቢያ በሞባይል ስልክ  እየተጠቀሙ አይደለም። (ኮሙኒኬሽን ኖቼ!) ስለዚህ “የክብር ደንበኞች” የሚለው ነው በደንብ የሚገልፀን (እኔም ሞባይል ተጠቃሚ እኮ ነኝ!)” በሌላ አነጋገር … የደንበኝነት ክብር የተሰጣቸው ግን አገልግሎት የማያገኙ እንደ ማለት ነው፡፡ (የክብር አባልነት ወይም የክብር ዶክትሬት በሉት!) አያችሁ … ዝም ብሎ የክብር ነገር ስለሆነ ብዙ የሚያሸልል ነገር የለውም፡፡ (በክብር ደንበኝነት መኩራት የሚሻ መብቱ ነው!) ምናልባት ግን እያንዳንዱ ባለሞባይል ሲቪው ላይ ሊያካትተው ይችላል - “የኢትዮ ቴሌኮም የክብር ደንበኛ ወይም “Honorary Customer of Ethio-Telecom” በማለት፡፡ እናላችሁ … 26 ሚሊዮን ደንበኞች አሉኝ የሚለው 26ሚ. “የክብር ደንበኞች” በሚል መስተካከል አለበት፡፡ (የዶክትሬት ድግሪና የክብር ዶክትሬት ለየቅል ናቸው!)
እግረመንገዴን … የመብራት ሃይል ኮርፖሬሽን ደንበኞችም “የክብር ደንበኞች” መባል እንዳለባቸው ላስታውስ እሻለሁ፡፡ (በጨለማ እያሳደረን “ደንበኞቹ” ልንሆን አንችልም!)
ጉደኛው የመብራት ሃይል ኮርፖሬሽን በቅርቡ በኢቴቪ ያስተላለፈውን ማስታወቂያ ሰምታችሁልኛል? (ብትሰሙማ እስካሁን ስቃችሁም አታባሩ ነበር!) የመብራት ሃይል ማስታወቂያ ምን መሰላችሁ? ከሌሊቱ 6 ሰዓት በኋላ ኃይል ስለሚቋረጥ “የክብር ደንበኞቹን” የቅድምያ ይቅርታ የሚጠይቅ ነው፡፡ (የይቅርታም ቀብድ አለው ለካ?) እናላችሁ … ቁጭ ብለን መብራት እንዳሻው ቦግ እልም ሲል ያልቀረበ ይቅርታ ከተኛን በኋላ ለሚጠፋው ይቅርታ መጠየቁ ግርም ያሰኛል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ግን ለደንበኞች አይሰራም- ምናልባት “ለክብር ደንበኞች” እንጂ፡፡
እኔ የምላችሁ … የአሁኑ ሳይሆን የወደፊቱ የጦቢያ የኃይል ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን የሚነግረን “አዋቂ” ጠፋ አይደለ?! (“ኃይል” ስል “ሥልጣን” ማለቴ አይደለም!) ከምሬ ነው … ከኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ እስከ አገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ድረስ ይሄን ነገር እኮ አያውቁትም (እነሱ ጠንቋይ - አይቀልቡ!) እናላችሁ … በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ፕሮፌሽናል የዕጣ ፈንታ ተንባዮችን (Fortunetellers) በኢንተርኔት ማሰስ ጀምሬያለሁ። ግን ዕድሜ ለቴሌኮም! አሁን ተቋርጧል (ቢሮዬ ኢንተርኔት ከእነ አካቴው ከጠፋ ሁለት ሳምንቱን ሊይዝ ነው!)
የሆኖ ሆኖ ግን ፍለጋዬ ይቀጥላል (“ፍለጋው አያልቅም” አለ ዘፋኙ!) እኔ የምላችሁ … “የምርጥ ከተሞች ፍለጋው” እንዴት እየሄደ ነው? በባህር ዳር እየተከበረ ያለውን “የከተሞች ሳምንት” ማለቴ ነው፡፡ መቼም “Top 10 Cities” በሚል አስሩን የኢትዮጵያ ምርጥ ከተሞች ማወቅ የምንችልበት በዓል እንደሚሆን “ቁርጠኛ እምነት” አለኝ፡፡ በነገራችሁ ላይ እኔ “የከተሞች ሳምንት” መክፈቻ በዓልን የተመለከትኩት በኢቴቪ ነበር - ከባልንጀራዬ ጋር፡፡ እናላችሁ … ባልንጀራዬ አክሮባት ሲሰሩ የነበሩ የባህርዳር ታዳጊዎችን አይቶ “የደርግን 10ኛ ዓመት የአብዮት በዓል አስመሰሉት እኮ!” አይል መሰላችሁ! (እኔ ደሞ ክው አልኩላችኋ!) እናም እንዲህ አልኩት “አይሁን እንጂ መምሰሉ ችግር የለውም!” (ደንግጬ እኮ ነው!)  የይምሰል ፈገግታ አሳየኝና የጨዋታ ርዕሰ ጉዳዩን ቀየረ - ባልንጀራዬ፡፡ የዚያኑ ዕለት አንድ የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊ ስለ ከተሞች ቀን በእንግሊዝኛ አጭር “ማብራሪያ” ሰጥተው ነበር (ማብራሪያው ሌላ ማብራሪያ ይፈልጋል!) እናም ባልንጀሬ ገብቶት እንደሆነ ስጠይቀው ምን አለኝ መሰላችሁ? “ተሸውደሃል እንግሊዝኛ የተናገሩ መስሎህ ነው?” አለኝ እየሳቀብኝ፡፡ በጣም ተናድጄ “እና ምንድነው ታዲያ?” አልኩት፡፡ “እኔ ምን አውቃለሁ” ብሎ እንደገና ሳቀብኝ፡፡ እኔ ግን ይሄው እስከዛሬ የተናገሩትን የሚፈታልኝ አላገኘሁም፡፡ (ፍለጋው ግን አያልቅም!)
እናንተ … በሳኡዲ ያሉ ዜጐቻችን ላይ የተፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በጣም ያሳዝናል አይደል? (ሳኡዲ እንዲህ ሲኦል ናት እንዴ?) ወገኖቻችን ከደህና አገራቸው ወጥተው መከራቸውን በሉ እኮ!! (ገንዘብ አጣን እንጂ አገር እኮ አለን!) “ገንዘብ የለም እንጂ ገንዘብ ቢኖርማ … ወይ አገር ወይ አገር ወይ አገር ጦቢያ” … ለማለት ዳድቶኝ ነበር። በነገራችሁ ላይ እስካሁን ወደ 12ሺ ገደማ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ነው (ቃል በቃል የተቀዳ!) የመ/ቤቱ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ “አሁን የዜጐቻችንን ደህንነት ለመታደግ ሙሉ ትኩረታችንን ስደተኞችን ወደ አገራቸው በመመለስ ተግባር ላይ አድርገናል። የደረሰባቸውን በደልና ጉዳት በተመለከተ ዜጐች ከተመለሱ በኋላ የምናጣራው ይሆናል” ነው ያሉት ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፡፡ እኔም በዚህ እስማማለሁ (ባልስማማም ለውጥ አላመጣማ!) እንዲያም ሆኖ ግን አንዳንድ ወሳኝ ጥያቄዎችን መሰንዘራችን አይቀርም (ኢህአዴግ የታገለለት ህገመንግስታዊ መብታችን ነዋ!) እናም ጥያቄያችን … “ይሄ ሁሉ ቀውጢ (Chaos) እስኪፈጠር በሳኡዲ የሚገኘው ኤምባሲያችን የማንን ጐፈሬ ሲያበጥር ነበር?” የሚል ነው፡፡ ችግሩ ከመከሰቱ በፊትስ መከላከል አይቻልም ነበር? (የማይቻል ነገር የለም አቦ!) “ከልብ ካለቀሱ …” ነው ነገሩ፡፡  
ከጥቂት ወራት በፊት እዚሁ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዘገባ፤ በሳኡዲ የሚገኙ ህገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤ ህጋዊ ለመሆን የሚያስችላቸውን ፈቃድ ለማግኘት እዚያ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፓስፖርት ቢጠይቁም ሊሰጣቸው ባለመቻሉ የሳኡዲ መንግስት ያስቀመጠው ቀነ ገደብ እየደረሰ መሆኑን ገልፀው ነበር (እንደ አቤቱታ!) ኤምባሲው ምላሽ ሲሰጥ ምን አለ? “ከአገር ቤት ፖስፖርት ታትሞ አልመጣልኝም!” (“የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” አሉ!) ኤምባሲው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ገንዘብ ካላዋጣችሁ ፓስፖርት አናድስም እንዳላቸው የገለፁ ስደተኞች እንደነበሩም አይዘነጋም፡፡ እንደውም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይሄን በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ በግዳጅ ገንዘብ አዋጡ የሚለው አሰራር ህገ ወጥ እንደሆነ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ተከበው ነው የሳኡዲ መንግስት ህገወጥ ስደተኞች ህጋዊ እንዲሆኑ የሰጠው የጊዜ ገደብ (የይቅርታ ጊዜ) የተጠናቀቀው፡፡ እናም ዜጐቻችን ለሞት፣ ለእስር፣ ለድብደባና ለዘረፋ የተጋለጡት፡፡ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂው ኤምባሲው ነው ለማለት ተጨማሪ መረጃና ጥናት ያስፈልጋል፤ ሆኖም መጠየቁ ግን አይቀርም (ሃላፊነት አለበታ!) እርግጥ ነው እያንዳንዱ ስደተኛ ወዶ ለገባበት ምርጫ ተጠያቂ እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ ግን ደግሞ የተሰደዱት ከድህነት ለማምለጥ መሆኑም ሊጤን ይገባል (ራሱ ኢህአዴግ ድህነትን ተረት አደርጋለሁ ይል የለ!) ለነገሩ ራሱ ኢህአዴግም ያልተሰደደው እኮ ሥልጣን ላይ ስለሆነ ነው!
እኔ የምለው ግን … በየአገሩ ያሉ ዲፕሎማቶቻችን ለወገኖቻቸው የሚቆረቆሩ ይመስላችኋል? (ነገር መጠምዘዝ አያስፈልግም!) ለመሆኑ ኢህአዴግ አምባሳደሮችን ሲሾም በምን መስፈርት ነው? (የፖለቲካ ታማኝነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው!) አንዳንድ ሃሜቶች ግን ይናፈሳሉ… የአምባሳደርነት ሹመት ለኢህአዴግ አባላት እንደ እረፍት የሚቆጠር ነው የሚሉ፡፡ ከረዥም አመት የመንግስት ሃላፊነት (አገልግሎት) በኋላ የሚታደል እንደማለት፡፡ እናም ሃሜቱ ድንገት እውነት ከሆነ ደግሞ … በአምባሳደርነት የሚሾሙት የደከማቸው ባለስልጣናት ናቸው ማለት ነው (የመተካካት ተረኞች!) መቼም ለምን ደከማቸው አይባልም አይደል? እንዴ 17 ዓመት በትግል ሜዳ፣ ከ20 ዓመት በላይ ደግሞ በልማት ሜዳ “የፈጉ” እኮ ናቸው፡፡ እናም በስደት ላይ የሚገኙ ዜጐቻቸው ጉዳይ ብዙም ባያሳስባቸው አይፈረድባቸውም፡፡ ጥፋተኛው ግን ሿሚው ነው (ራሱ ኢህአዴግ!)
በነገራችሁ ላይ … በመላው ዓለም ያሉ የጦቢያ ልጆች በሳኡዲ የተፈፀመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች በሰልፍ መቃወማቸው ያኮራል፡፡ በአዲስ አበባ የተሞከረው ተቃውሞ መክሸፉ ደግሞ ቅር ያሰኛል። አንዳንድ ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞች “ለዚህ ለዚህማ ሳኡዲ ይሻላል!” እንዳሉም ሰምተናል። ፖሊስ በበኩሉ፤ የሳኡዲን ኤምባሲ ሰብረው እንዳይገቡ ያደረግሁት ጥንቃቄ ነው ብሏል (ያለ ዱላ መጠንቀቅ አይቻልም ነበር) ደሞም እኮ ተመሳሳይ ተቃውሞ በተደረጉባቸው የዓለም አገራት ሁሉ የሳኡዲ ኤምባሲዎች አሉ፡፡ እዚያም ተቃውሞው ተካሂዷል፤ ሰልፈኞችም ኤምባሲ ሰብረው አልገቡም፡፡ (መንግስታችን “ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችንን” ዘነጋው ልበል?!) ለማንኛውም ግን ህገ መንግስታዊ መብታችን እንደ ቴሌኮም ኔትዎርክ ባይቆራረጥ ይመከራል፡፡ (ይመረጣልም!) ያለዚያ ግን እኛም ለኢህአዴግ “የክብር ህዝቦች” መባላችን አይቀርም - እንደ ቴሌኮም “የክብር ደንበኞች!” አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች “ብትሆኑ ምን ችግር አለው?” ይሉ ይሆናል፡፡ ግን ከባድ ችግር አለው፡፡ (“አደጋ አለው” አሉ!) ለምን መሰላችሁ? “የክብር ህዝቦች” ግብር አይከፍሉማ! ያለ ግብር ደግሞ ኢህአዴግ አንዲትም ቀን አያድርም፡፡ (ያለ ግብር የኖረ መንግስት የለማ!)

Sunday, 24 November 2013 17:36

አረቦችና ስደተኛ ዜጐች

ማንኛውም ሀገር በህገወጥ መንገድ የራሱ ዜጐች ያልሆኑ ሰዎች ወደ ግዛቱ በማናቸውም አይነት መንገድ ዘልቀው እንዳይገቡ አቅሙ የፈቀደውን ያህል ጥበቃና ቁጥጥር በድንበሩ ላይ ያደርጋል፡፡ በዚህ መሃል ጥበቃና ቁጥጥሩን ጥሰው ወደ ግዛቱ ለመግባት ሲሞክሩ አሊያም ገብተው ያገኛቸውን ሰዎች በህገወጥነት ወንጀል ከሶ እንዳወጣው ህግና ደንብ መሠረት ተገቢ ነው ያለውን ቅጣት ወይ በእስር፣ ወይም ከሀገሩ በማስወጣትና ወደ መጡበት በመመለስ ወይም በሌላ የቅጣት አይነት ይቀጣል፡፡ የተለያዩ የአለም ሀገራት፣ በተለያየ ወቅትና አጋጣሚ ይህንን ሲያደርጉ በሚገባ አይተናል፡፡
ይህን የመሰለውን ጉዳይ በተመለከተ ሌላም አንድ አብይ ጉዳይ አለ፡፡ ማንኛውም ሀገር እንኳን በህገወጥ መንገድ ወደ ግዛቱ የገቡትን ስደተኞች ይቅርና በወግ በማዕረግ የገቡትንም ቢሆን “የአይናችሁን ቀለም አልወደድኩትም” የሚል መናኛ ምክንያት በማቅረብ ብቻ ከግዛቱ ለማስወጣት መብቱ ጥብቅና በእጁ ነው፡፡ በረጅሙ የአለማችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተለያዩ ሀገራት በተለያየ ጊዜና አጋጣሚ ይህን መሰሉን ድርጊት ለበርካታ ጊዜያት ሲፈጽሙት ኖረዋል፡፡
ይህን ድርጊት አለማቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያደርገው አንዱ ዋነኛ ነገር የሀገራቱ የድርጊት አፈፃፀም ሁኔታ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሀገራት ከግዛታቸው የሚያባርሯቸውን ህገወጥ ሆነ ህጋዊ ስደተኞች ሰብአዊ መብትና ክብራቸውን ለመጠበቅ የቻሉትን ሁሉ ሲያደርጉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ስደተኞቹን ማናቸውንም አይነት ዘዴ ተጠቅመው ማባረራቸውን እንጂ ለሰብአዊ መብታቸውና ክብራቸው መጠበቅ ቁብ የለሽ ናቸው፡፡
ሳኡዲት አረብ በህገወጥ መንገድ ወደ ግዛቷ ዘልቀው የገቡ ስደተኞኖች ህጋዊ እንዲሆኑ የሁለት አመት የጊዜ ገደብ  አስቀምጣላቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በህገወጥ መንገድ ወደ ግዛቷ የገቡ የየመን፣ የባንግላዲሽ፣ የስሪላንካ፣ የፓኪስታን፣ የህንድ፣ የፊሊፒንስ፣ ወዘተ ስደተኞች ህጋዊ መሆን ችለዋል፡፡
የዚህኑ ያህል ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህገወጥ ስደተኞች፤ ህጋዊ መሆን ሳይቻላቸው ቀርቷል፡፡ ሁኔታውን በሚገባ የሚያውቁ የስደተኛ እርዳታ ባለሙያዎች፤ ከእነዚህ ስደተኞች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ኢትዮጵየውያን ስደተኞች መሆናቸውን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ያወጣው የሁለት አመት የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ በወሰደው አስገዳጅ የሃይል እርምጃ፤ በተለይ በህገወጥ ኢትዮጵየውያን ስደተኞች ላይ የተፈጠረው ሁኔታ ያረጋገጠልን እውነታም ይህንኑ ነው፡፡
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት አውጥቶት በነበረው የጊዜ ገደብ ውስጥ ህጋዊ መሆን ባልቻሉ ስደተኞች ላይ ሊወስደው የሚችለውን አስገዳጅ የሃይል እርምጃ በልባምነት አስቀድመው መገመት የቻሉ እንደ የመን፣ ፊሊፒንስ፣ ስሪላንካ፣ ባንግላዴሽና ፓኪስታን ያሉ ሀገራት አስፈላጊውን ርብርብ በተገቢው ትጋት በማከናወን፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህገ ወጥ ስደተኞቻቸውን ወደ ሀገራቸው በመመለስ ዜጐቻቸውን ከከፍተኛ ስቃይና መከራ መታደግ ችለዋል፡፡
በሳኡዲ አረቢያ ከሚገኙትና በወጣው የጊዜ ገደብ ውስጥ ህጋዊ መሆን ካልቻሉ ህገወጥ ስደተኞች ውስጥ ከሁሉም በበለጠ ቁጥርና ከሁሉም እጅግ በከፋ ሁኔታ የሳኡዲ አረቢያ ፖሊስና የሳኡዲ ስርአት አልበኛ የመንደር ዱርዬዎች አሰቃቂ የግድያ፣ የድብደባ፣ የአስገድዶ መድፈር፣ የዘረፋና፣ የእስር ሰለባዎች የሆኑት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው፡፡
የሳኡዲ ፖሊስና ህገወጥ የመንደር ዱርዬዎች በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የፈፀሙት እጅግ አስከፊ ግፍና በደል በሳኡዲ አረቢያ የፖለቲካና የማህበራዊ ኑሮ ታሪክ ላይ ለረጅም ዘመን እጅግ መጥፎ የሆነ ጥቁር ጥላውን አጥልቶ የሚኖር፣ በዚህ የሰለጠነ ዘመንና፣ የሰለጠነ አለም ውስጥ ይደረጋል ተብሎ የማይገመት እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት እንኳን ህገወጥ ናቸው ላላቸው የሌላ ሀገር ዜጐች ይቅርና ለራሱ ሀገር ዜጐች የሰብአዊ መብት መከበር ምንም አይነት ደንታ የሌለው መንግስት መሆኑ፣ መላው አለም ያወቀውና ፀሀይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያላንዳች ጥበቃና ከለላ በእጁ የሚገኙትን ስደተኞች በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ያን የመሰለ እጅግ ወራዳ ግፍ፣ ድፍን አለሙ ሁሉ እያየው በጠራራ ፀሀይ ይፈጽማል ተብሎ ጨርሶ አልተገመተም ነበር፡፡
በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር ከፍተኛ የውርደትና የመጠቃት ስሜት የፈጠረባቸው ይህ የሳኡዲ አረቢያ እንስሳዊ ድርጊት ነው፡፡ አለመጠን ያንገበገባቸው ደግሞ እንደ ሌሎቹ ሀገራት መንግስታት የኢትዮጵያ መንግስት እነዚያን የግፍ አበሳ የወረደባቸውን ዜጐች፣ ባፋጣኝ ለመታደግ አሳይቷል ያሉት ከፍተኛ ዳተኝነት ነው፡፡ የተሰማቸውን ከፍተኛ ቁጣም ከአዲስ አበባ እስከ አሜሪካና ካናዳ፣ ከአፍሪካ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ በአንድነት ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ፤ የሳኡዲ አረቢያን መንግስት በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በፈፀመው እጅግ ነውረኛ ድርጊት ባወገዙበት በእነዚህ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች ውስጥ ምናልባትም በሁሉም በሚባል መልኩ ያነሱት አንድ አብይ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን እንደተሰማው ዓይነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዳይፈፀምባቸው ምን ሰርተዋል? ምንስ ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አድርገዋል የሚለው ነው፡፡ ሳኡዲ አረቢያ በእስልምና ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገውን የሙስሊሞችን ስደት ወይም ሂጅራና ይህንንም ተከትሎ የእምነቱ መስራች አባት የሆኑት ነብዩ መሀመድ (ሰ.ወ.ወ)፤ ስለ ኢትዮጵያ የተናገሩትንና መላ ሙስሊሞች እንዲፈፅሙት ያዘዙትን ትዕዛዝ እንዲያስታውሱ ያቀረቡት ጥያቄ ወይም ማሳሰቢያ ነው፡፡ ሆኖም ይሄን ነገር አረቦቹ እንዲያጤኑ ምን ያህል ከልብ ተንቀሳቅሰናል ነው-ጥያቄው፡፡ ሌላው ደግሞ የአገራችን ዲፕሎማቶች ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን እንደተሰማው ዓይነት ኢሰብዓዊ ድርጊት እንዳይፈፀምባቸው ምን ሰርተዋል? ምንስ ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አድርገዋል የሚለው ነው፡፡ በመጨረሻው ሰዓት መንግስት የተረባረበበትን ስደተኞችን የማስመለስ ጥረት ቀድሞውኑ ለማድረግ ምን ያዘው? ብለንም መጠየቃችን አይቀርም፡፡ አሁንም ቢሆን ካለፈው ስህተት ተምረን በየአረብ አገራቱ ላሉ ዜጐቻችን የተሻለ ጥበቃና ከለላ ማድረግ ተገቢ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

                     ከሣምንት በፊት በአፍሪካ ህብረት የተካሄደውን የአፍሪካ ሚዲያ የመሪዎች ፎረም፣ ለእኛው ኢቴቪም፤ የማይረሡ ዝግጅቶችን፣ የሚያሥደምሙ የጋዜጠኞች ማህበራት ቅንብርብር መድረኮችን፣ “ለምንወደውና ለሚወደን ህዝቦቹ” እንዲያሣይ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖለት አልፏል፡፡ የሚዲያ ፎረሙን ምክንያት በማድረግ፣ ሙያዊ ሣይሆን ተቋማዊ የሚመሥል የአቋም መግለጫ ለማስተላለፍ፣ ለአቅመ ጋዜጠኝነት የበቁ የመሠሉት የጋዜጠኞች ማህበራት፣ ሥለ ኢህአዴግ የፕሬሥ ነፃነት አከባበር ሲያሥተነትኑ፣ ስለየትኛዋ አገር እንደሚናገሩ ግራ ተጋብቼ ነበር፡፡
የጋዜጠኞች ማህበራት በጥምረት፣ የፕሬሥ ነፃነትን በማክበር ጉዳይ ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ሁሉ ምሣሌ ልትሆን እንደምትችል አድርገው ሲብራሩ ሣይሆን “ሲያቅራሩ”፣ “ኧረ ህዝብና መንግሥት ባትፈሩ፣ ቆምንለት የምትሉትን ራዕይ ፍሩ” የሚል አንድ የኢህአዴግ ታማኝ ካድሬ እንዴት ይጠፋል? ያሥብላል፡፡ የማህበራቱ መሪዎች በኢቴቪ ሢታዩ ከንግግራቸው አነጋገራቸው፣ ከልብ ባይነታቸው፣ ልበ ሙሉነታቸው ይገርማል፤ እንደውም አንባቢያን ካልታዘባችሁኝ፣ “ጋዜጠኞቹ” በልበ ሙሉነት ያቀረቡት ንግግር ከማስረገም አልፎም፣ “አሥቀንቶኛል” ብል ደስ ይለኛል፤ እውነቴን ነው … መንግሥት እራሡ ያልካደው የኢትዮጵያን የፕሬስ ጣጣ እንከን የለሽ አድርጐ የማውጋት ድፍረት፣ ያውም በመላው ዓለም በሚተላለፍ የቴሌቪዥን መስኮት ፊት ቀርቦ በልበ ሙሉነት የመግለጽ “ነፃነት” በርግጥም የሚያሥቀና ይመሥለኛል፡፡ ታዲያ፣ በጋዜጠኞቹ መግለጫ እየተገረምኩ፣ የእኔ የመረጃ ድርቀት ወይሥ የእነሡ ድፍረት እንዲህ የሚያብከነክነኝ? እያልኩ ከራሤ ጋር ሣወጋ ቆይቼ ነበረ፡፡ ደግነቱ ግን የዛሬ ሣምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ፣ “የጋዜጠኞች” ማህበራቱን ኢህአዴግ ራሱ ታዝቧቸዋል!” የሚል ርዕስ ሣነብ፣ እራሴን ከመውቀሥ ተገላገልኩ፡፡ ወዲያው በጋዜጣው የፊት ለፊት ገጽ የተጠቆመውን ርዕስ ዱካ ፍለጋ ገፆች ገላለጥኩ፡፡
“የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያሥታውቃል” እንዲሉ፣ በተገረምኩበት ርዕስ፣ ሥር የቀረበው ጽሁፍ በሚገባ ቀልቤን ገዝቶት አገኘሁት፡፡ በምፀታዊ የፖለቲካ አሽሙራቸው የታወቁት አቶ ኤልያስ፣ ዛሬም የጋዜጠኞቹን ስሜታዊ መግለጫ፣ በተጠያቂያዊው መረጃ አለዝበው፣ በፈገግታ ሞሽረው ነበር ያቀረቡት፡፡
የፖለቲካ በፈገግታው አምደኛ፣ የጋዜጠኞች ማህበራቱን መግለጫ የጋዜጠኞች ሣይሆን የ‘አብዮታዊ መንግሥት’ ወይም ‘ድርጅት’ ነበረ የሚመስለው በማለት፣ መግለጫ አቅራቢ ጋዜጠኞች፣ የመድረክ ትወናውን ብቻ ሣይሆን፣ ቃለ ተውኔቱንም ከኢህአዴግ ጽንፈኛ ካድሬዎች የኮረጁት እንደሚመሥል በወጉ ነው ያሥተነተኑት፡፡
የተባለውን ለማስረገጥ የአምደኛው ምፀታዊና አሽሙራዊ ትችት እንደሚከተለው ማጣቀስ ይቻላል፤ የጋዜጠኞች ማህበራቱ ካቀረቧቸው ጽንፍ ላይ የቆሙ መግለጫዎች መካከል፣ “አንደኛው ደግሞ ከኢህአዴግ ቃል በቃል የተኮረጀ ነው (ኮማ ሣይቀር!) ልዩነቱ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ‘በኢትዮጵያ ውስጥ ከሙያቸው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞች የሉም’ የሚል ምላሽ ሲሰጥ ደንፍቶ አያውቅም፡፡ እነሱ ግን ቀላል ቀወጡት! አገር ይያዝልን እኮ ነው ያሉት፡፡ ቦታው ሥላልተመቻቸው ነው እንጂ ሽለላና ቀረርቶ ሁሉ ዳድቷቸው ነበር፡፡ (ኢህአዴግ ራሱ እኮ ሳይታዘባቸው አይቀርም) እኔማ ምነው በገመገመልኝ ብዬ ነበር፡፡ ለካሥ የኢህአዴግ አባል አይደሉም (ናቸው እንዴ?)”  በአሽሙራዊ መጣጥፉ ላይ በቅንፍ ውስጥ የቀረቡት ገለፃዎች የምር እያሣቁ ዘና አድርገውኛል፡፡ ለነገሩ በመጀመሪያ ቅንፍ ውስጥ የሰፈረው ገለፃ፣ ማለቴ “ኮማ ሣይቀር!” የሚለው ከማዝናናት አልፎ በትዝታ ውስጥም አስምጦኝ ነበረ፡፡ “ኮማ ሣይቀር!” የሚለውን ከማን ንግግር ላይ ነበር የሰማሁት የሚለው ትንሽ አሥቆዘመኝ፡፡ በኋላ ግን፣ ነፍሣቸውን ይማር ከአቶ መለስ ዜናዊ ንግግር ውሰጥ እንዳዳመጥኩት ትዝ አለኝ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ንግግሩን ለማስታወሥ ሥሞክር ርዕሠ ጉዳዩ፣ “የፀረ ሽብር አዋጁ” ነበር፡፡
አቶ መለስ፣ ስለ ፀረ ሽብር አዋጁ በፓርላማ ተገኝተው መግለጫ ሲሰጡ፣ “የፀረ ሽብር አዋጁ ህገ መንግሥቱን ይጥሣል፤ አንዳንድ ጽንፈኛ ካድሬዎችም ላልተገባ ተግባር ያውሉታል፤ የዜጐች ሰአብዊ መብቶች እንዲገሰግሡ የህግ ድጋፍ ይሆናል …” የሚሉ የተለያዩ ሙግቶች ቀርበውባቸው ነበረ፡፡ ባለ “ራዕዩ መሪ” ታዲያ አፍ የሚያዘጋ መልሥ አብሠለሠሉና “የፀረ ሽብር አዋጁ ቃል በቃል ከምዕራባዊያኑ የተገለበጠ ነው - ኮማ ሣይቀር!” የሚል ምላሽ መሥጠታቸውን አልረሣውም፡፡
እናም፣ “ኮማ ሣይቀር” የሚለው፣ “የኢህአዴግ አባል አይደሉም እንዴ?” ከሚለው ጠያቂ አሽሙር ጋር ተጣምረው፣ “ኢህአዴግ ራሱ ታዝቧቸዋል!” በሚል መሪ ቃል መቋጨቱ፣ የጋዜጠኛ ማህበራቱን አቋም የምር እንድንጠይቅ ያሥገድዳል፡፡ የማህበራቱ መሪዎች፣ ስብዕናን ጥያቄ ውስጥ የሚጥለውም ይመሥላል፡፡ “በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገራት የበለጠ ተከብሯል” የሚለው ስሜታዊና ደፋር አቋም፣ እንደተባለውም በኢህአዴግ “ትዝብት ላይ የሚጥል ቅሌት” መሥሎ የሚታይ አይመሥልም ማለት ሁሉ ይከብዳል፡፡
ኢህአዴግ በባለ ራዕዩ መሪው፤ በአቶ መለስ ሀሣብ የተጠመቀ የማያወላውል ድርጅት ከሆነ በርግጥም፣ “ወላዋይና አድርባይ” ባህርያትን፣ በፅኑ ይቃወማቸዋል ብሎ ማሠብ ይቻላል፡፡ ባህርያቱን ከተቃወመ ደግሞ፣ የባህርያቱ መገለጫ የሆኑ ተክለ ሰውነቶችንም፣ በተለይ ለእርሡ የሚጠቅሙት ከሆነ በፊት ለፊት ላይቃወማቸው ይችላል፤ የቀደመ መሪውን “ራዕይ” የሚያሥፈጽም ድርጅት መሆኑ አፋዊ ሣይሆን ልባዊ ከሆነ ደግሞ በፊት ለፊት የማይቃወማቸው አድርባይ ሰዎችን ቢያንሥ ሊታዘባቸው እንደሚችል ግን ግልፅ ነው፡፡ ካልሆነ፣ የመሪውን የአደራ ቃል የበላ፣ ራዕያቸውን ማስቀጠል የማይችል ተክለ አቋም እየገነባ ነው ሊባል ሁሉ ይችላልና፡፡
ለዚህ ሀሣቤ ደግሞ፣ የአቶ መለሥ ራዕይ፣ “የጋዜጠኞች ማህበራቱን አቋም” እንደሚቃወም ማስረገጥ ብቻ የሚበቃ ይመሥለኛል፡፡ አቶ መለስ በአንድ ወቅት ስለሚወዱትና ስለሚጠሉት ሰው ሁኔታ ሲጠየቁ የመለሱትን ምላሽ ቃል በቃል መጥቀሥ ይቻላልና፤ “ቢከፋም ቢለማም አቋም ያለው ሰው አከብራለሁ፡፡ አቋም የሌለውና ወላዋይ ሰው በአጋጣሚ እንኳን ደጋፊ ቢሆን ብዙም አይመቸኝም፡፡ ስለዚህ ለኔ የመጀመሪያና ዋናው መለኪያ አድርጌ የምወስደው፣ አንድ ሰው የሚያምንበትንና የማያምንበትን ተገንዝቦ፣ አቋሙን በሚገባ የሚያውቅና ላመነበት በፅናት የሚታገል ከሆነ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰው ነው ጥሩ ሰው የምለው፡፡ ፅኑ አቋም ብቻ ሣይሆን ፅኑና ጥሩ አቋም ያለው ሰው ደግሞ የበለጠ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡”

የሳውዲ ልኡሎችና ባለስልጣናት በአገሪቱ ዋና ከተማ ሪሃድ የሚገኙ 18ሺ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ሰሞኑን እንደጐበኙ ተገለፀ፡፡
በሪያድ ከተማ በ“ፕሪስት ኖር ኢስት ሪሃድ ዩኒቨርሲቲ” ጊዜያዊ መጠለያ ተሰጥቷቸው የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን የጐበኙት ልኡል ካህሊድ ቢን ባንዳር አብድልላዚዝና ወንድማቸው ልኡል ተርኪ ቢን አቡድሃል ቢን አብዱል አዚዝ ሲሆኑ ልኡሎቹ ኢትዮጵያውያኑ በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከልኡሎቹ ጋር በሳውዲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የሳውዲ መንግስት ባለስልጣናት እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአሁኑ ሰአት በስደተኞች ላይ የሚደርሰው እንግልትና ስቃይ ከመጀመሪያዎቹ ቀናት ረገብ እያለ መምጣቱን የጠቆሙ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን፤ ለዚህም ምክንያቱ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን “የወገኖቻችን ጥቃት ይቁም” በማለት በየአገራቱ በሚገኙ የሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ ጫና በመፍጠራቸው ሳይሆን እንደማይቀር ዘግበዋል፡፡
በሳኡዲ በሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን እንግልትና ስቃይ በተመለከተ በአዲስ አበባ የሚገኘው የሳኡዲ አረቢያ ኤምባሲ ማብራሪያ እንዲሰጠን ብንጠይቅም፣ ማተምያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ ከኤምባሲው ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡  

Published in ከአለም ዙሪያ

ጥንት አንድ አዋቂ ሰው ነበር ይባላል፡፡ በመጪው ዓመት ምን እንደሚከተል ያውቃል አሉ፡፡ አንድ ቀን ንጉሡ የ አዋቂ መጥቶ መጪውን እንዲተነብይ ያስጠራውና ወደ ሸንጐ እየመጣ ሳለ፤ አንድ እባብ ያገኛል፡፡ “ንጉሡ ትንቢት ተናገር ብለውኛል፤ ምን ልበል?” አለና ጠየቀው፡፡ እባቡም፤
“መጪው ጊዜ ጦርነት ስለሆነ ፀልዩ! በላቸው” አለው፡፡
አዋቂው ሸንጐ ቀርቦ እባቡ እንዳለው፤ ለንጉሡ ተናገረ፡፡ “ያለው ዕውነት ነው” አሉና ንጉሡ ሸልመው ሸኙት፡፡ አዋቂው ወደቤቱ ሲመለስ ያን እባብ አገኘው፡፡ በጦሩ ወጋውና መንገዱን ቀጠለ፡፡
በሁለተኛው ዓመት እንደገና ንጉሡ አዋቂውን አስጠሩት፡፡ እዚያው ቦታ የቆሰለውን እባብ አገኘው፡፡
እባቡም፤ “ባለፈው ዓመት መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ጠይቀኸኝ፤ ነግሬህ፣ ወግተኸኝ ሄድክ፡፡ ሆኖም አሁንም እነግርሃለሁ፡፡ ይህ ዓመት የበሽታ ዓመት ነውና ፀልዩ በላቸው” አለው፡፡
አዋቂው ወደ ሸንጐ ሄደና የበሽታ ዓመት እንደሚሆን ተናገረ፡፡ ንጉሡም “ባለፈው ዓመት የተናገረው ዕውነት ስለሆነ ዘንድሮም የተናገረው ዕውነት መሆን አለበት፡፡ በሉ፤ ሸልሙና ሸኙት” አሉ፡፡
አዋቂው ሲመለስ ያንን እባብ አገኘው፡፡ በድንጋይ መትቶ ወግሮ ወግሮ መንገዱን ቀጠለ፡፡
በሶስተኛው ዓመት እንዲሁ አዋቂው ሸንጐ ተጠራና ሄደ፡፡ መንገዱ ላይ እዛው ቦታ እባቡን አገኘው፡፡
“ዘንድሮስ ምን ብል ይሻለኛል?” አለው፡፡
“ባለፈው ዓመት መክሬህ፣ ተናግረህ፣ ተሸልመህ ስትመለስ በድንጋይ መትተኸኛል፡፡ ሆኖም አልተቀየምኩህም፡፡ በዚህ ዓመት የእሳት ዘመን ነውና ፀልዩ በላቸው” አለው፡፡
ወደንጉሱ ሄዶ “ዘንድሮ የእሳት ዘመን ነው” አላቸው፡፡
ንጉሡም፤ “ባለፉት ሁለት ዓመታት የተናገረው ዕውነት ስለሆነ፤ ዘንድሮም ያለው ዕውነት መሆን አለበት፡፡ ሸልሙትና ይሂድ” አሉ፡፡
አዋቂው ሲመለስ እባቡን አገኘው፡፡ አሁን ግን መምታት ሳይሆን በእባብ ሊያቃጥለው ሞከረና መንገዱን ቀጠለ፡፡
በቀጣዩ ዓመት ለአራተኛ ጊዜ ንጉሡ አስጠራው፡፡ አዋቂው መንገዱ ላይ እባቡን አገኘው፤
“ዘንድሮስ ምን ልበል?” አለው፡፡
እባቡም፤ “ዘንድሮ የጥጋብ ዘመን ስለሆነ ፈንድቁ! በላቸው” አለው፡፡
ንጉሡ የጥጋብ ዘመን መሆኑን ሲሰሙ “እስከዛሬ የተናገረው ምንም መሬት ጠብ የሚል ነገር አልነበረውም፡፡ ዘንድሮም ዕውነት ስለሚሆን በርከት አድርጋችሁ ሸልሙልኝ” አሉ፡፡
አዋቂው ወደቤቱ ሲመለስ እባቡን አገኘው፡፡ በዚህ ጊዜ ግን በሀር የተንቆጠቆጠ ካባ አለበሰው፡፡
እባቡም፤
“የመጀመሪያው ዓመት የፍልሚያ ዘመን ነበረና በጦር ወጋኸኝ፡፡
በሁለተኛው ዓመት የበሽታ ዘመን ነበረና በድንጋይ ወገርከኝ፡፡
በሦስተኛው ዓመት የእሳት ዘመን ነበረና በእሳት አቃጠልከኝ፡፡
በአራተኛው ዓመት ግን የጥጋብ ዘመን በመሆኑ ካባ አለበስከኝ፡፡ እነሆ ጥበቤን ሁሉ ሰጥቼሃለሁ፡፡ ያ ይበቃሃል፡፡ አሁን ካባህን መልሰህ ውሰድ፡፡ የሰጠሁህ ጥበብ ከምንም ነገር በላይ ነው፡፡ ጥበቤን ሁሉ ውሰድ፡፡ ራሴ የነገርኩህን የነገ ዕጣ - ፈንታ፤ ራሴውም መጋራት ስላለብኝ ነው ያልተበቀልኩህ! በምንም ቁሳቁስ ልትተካው አትሞክር”  
                                                        *   *   *
ዕጣ-ፈንታችንን አናመልጥም፡፡ የዕጣ-ፈንታችን አካል ነን፡፡ የምንለው፣ የምናቅደው፣ የምንራዕየው ሁሉ የእኛው አካል ነው፡፡ በተናገርነው እንነገርበታለን፡፡ በደነገግነው እንቀጣበታለን፡፡ በደሰኮርነው እናፍርበታለን ወይም እንኮራበታለን፡፡ በተለይ መንግስት ስንሆን ባወጣነው ህግ እከሌ ከእከሌ ሳንል፣ ወገናዊና ኢፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ መተዳደርና መቀጣት አለብን፡፡
የመንግሥትነታችን ትልቅ ቁም ነገር የህዝብን ደህንነትና የሀገርን ህልውና መታደግ ነው፡፡ ይህ ዋና ኃላፊነት ነው፡፡ ህዝብ እንዳይሸበር፣ እንዳይጠራጠር፣ ዕምነት እንዳያጣ ማድረግ፤ በአገሩ፣ በመንግሥቱና በኃላፊዎቹ ላይ የመተማመን ስሜት እንዲያድርበት ያደርገዋል፡፡  
“የመንግሥት መኖር ዓላማው የህብረተሰቡን የተለያዩ ፍላጐቶች ለማርካት፣ አገርን ለማጠንከር መሆን አለበት፡፡ መንግሥታዊ ህጐችና ተቋሞቹም ዘለዓለማዊ ሳይሆኑ ይህንኑ ማህበራዊ ፍላጐት ለማስገኘት ሲባል ከህብረተሰቡ ዕድገት ጋር አብረው የሚያድጉና የሚለወጡ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ድህነት፣ ሰብአዊ ጉስቁልና፣ ሀዘንና ሰላም - የለሽነት ይቆራኘውና ለውድቀት ይዳረጋል” ይለናል የጥንቱ፣ የታህሣሥ 1953ቱ ንቅናቄ ተዋናይ፤ ግርማሜ ነዋይ (የታህሣሡ ግርግርና መዘዙ)
የህዝብን ችግር ቸል አንበል፡፡ የኋላ ኋላ ጣጣው ይመለከተናልና!
ለትናንሽ የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሔ ሳንሰጥ ወደ ውስብስብና ግዙፍ ችግርነት እንዲያድጉ ከፈቀድንና ቸልታችን ከበዛ፤ ያለ ጥርጥር ወደ ፖለቲካዊ ችግርነት ማደጋቸው አይቀሬ ነው፡፡
የወሎ ረሃብ እንደተነናቀ ወደ አብታዊ ማዕበልነት ተለወጠ፡፡ የሚሊተሪ ዲክታተራዊ አገዛዝ መናጠጥ፣ የቢሮክራሲያዊ በደል ማጠጥ፣ የሥልጣን መባለግና ያላግባብ መበልፀግ የአማጽያንን መፈልፈልና የተቃዋሚን ቁርጠኝነት መውለዱን ወለደ፡፡
ዛሬም የህዝብን ኑሮና የሀገርን ውስብስብ ችግሮች በወቅቱ የመፍታት ቅን ልቦና ከሌለ ዕጣ- ፈንታ ወዳዘዘው ውድቀት ማምራት ግድ ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዳይ የመንግሥት ዋንኛ ትኩረት የአንበሳውን ድርሻ ይውሰድ እንጂ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጐች ወዘተ የነገዋ አገራችን ዕጣ-ፈንታ ይመለከተናል ማለት ኤጭ የማይባል ነገር መሆኑን ልብ ማለት ደግ ነው!
“የህዝብ ችግር እየተባባሰ በሄደ ቁጥር፤ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እያወቀ እንዳላወቀ፣ እያየ እንዳላየ፣ በዝምታ መኖሩ ከባድ የህሊና ሸክምና ፈታኝ ጥያቄ ነው” ይላል ጄኔራል (መንግሥቱ ነዋይ፡፡)  
አቶ ብርሃኑ አስረስ “ማን ይናገር የነበረ…የታህሣሡ ግርግርና መዘዙ” በተባለው መጽሐፋቸው፤ ህዝብ ጭቆና ሲያንገፈግፈው ስለሚደርስበት ደረጃ ሲናገሩ፤
“የሕዝብን መነሳሳት ለማፍራት ብዙ ሙከራ ተደርጐ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ቀፎው ተነክቶበት የተሸበረ ንብና ተስፋውን ጨርሶ የተነሳ ሕዝብ ተመሳሳይ በመሆኑ፤ የተፈፀመው ሙከራ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ድሮው ተገዥነት ቦታው ለመመለስ አልቻለም…” ይሉናል፡፡
የአስተዳደር ብስለታችን፣ የዲፕሎማሲያችን ጥራት፣ ስለፓርቲና ስለ ሀገር ያለን ግንዛቤ፤ የምንመራውን ህዝብ አመኔታና ተቀባይነት የሚያስገኘው ቁልፍ ነገር መሆኑን መቼም ቢሆን መቼም እንወቅ፡፡ የህዝብን የልብ ትርታ፣ የሀገር ወዳዶችንና ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ድምጽ እንደገዝጋዡ ሳይሆን እንደ አጋዡ በማየት ማግባባት፣ ማስማማት፣ ማደራደር ከመሪዎቻችን የሚጠበቅ የብልህ እርምጃ ነው፡፡ ያለድካ

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በደረሰው ስቃይ ዙሪያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግስትን ድክመት መተቸታቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሐኖም በበኩላቸው፤ ዜጐቻችንን ለማዳንና ወደ አገር ቤት ለመመለስ እየተረባረብን ነው በማለት ጉዳዩ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆን እንደሌለበት ተናገሩ፡፡
ህገወጥ ደላሎች እንደ አሸን በመፍላታቸውና ኤጀንሲዎች በመበራከታቸው በርካታ ዜጐች ለስቃይና ለእንግልት መዳረጋቸውን የገለፁት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ በሳኡዲ የተከሰተውን ችግር በሚመለከት መንግስት ተመጣጣኝ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በስደተኛ ዜጐቻችን ላይ በደረሰው ስቃይ የሳኡዲና የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ ናቸው በማለት የሰጡት አስተያየት ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ በሰፊው መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፤ “መንግስት፤ ህገወጥ ናችሁ የተባሉ ዜጐቻችን ህጋዊ ተቀባይነት እንዲያገኙ፣ አልያም ወደ አገር እንዲመለሱና ህገወጥ ስደትን ለማስቀረት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡” ብለዋል ዶ/ር ቴዎድሮስ። ዜጐችን ለማገዝ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ጉዳዩን በፖለቲካ አጀንዳነት መጠቀም ተገቢ አይደለም ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ የወረደ፣ የረከሰ አካሄድ የኢትዮጵያዊነት ምልክት አይደለም ሲሉ ተችተዋል፡፡
በተለያየ አቅጣጫ የገቡና ለሃጂና ኡምራ ሄደው እዚያ የቀሩ፣ ለበርካታ ዓመታት ቁጥራቸው እየተበራከተ ዛሬ እስከ 80 ሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን በሳኡዲ እንደሚኖሩ የገለፁት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ ከ38 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ህጋዊ ፈቃድ የላችሁም የተባሉትን በሚመለከት አስቸኳይ በጀት በመመደብ በቀን ከ4ሺ በላይ ዜጐች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
በርካታ ዜጐች ላይ ጉዳት እንደደረሰና እስካሁን በተረጋገጠው መረጃ 3 ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን የተናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ “የሚሞቱና ጉዳት የሚደርስባቸውን ዜጎች በተመለከተ ከሳኡዲ ተወካይ ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፤ የህግ አማራጮችም ሊታዩ ይችላሉ፡፡” ብለዋል፡፡
መንግስት ጠንከር ያለ እርምጃ አልወሰደም በሚል የሚቀርበውንም ትችት በተመለከተ ተጠይቀው፣ መንግስት ትክክለኛውንና ተመጣጣኝ እርምጃ እየወሰደ ይቀጥላል ብለዋል።

Published in ዜና
Page 7 of 19