Monday, 18 November 2013 11:37

አስማተኞቹ እና ሚስጢራቸው

እኔ የተረዳሁትን ማንም ስላላወቀ እንጂ ሀሳቡ ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ ንግድ ማለት ቅይይር ማለት ነው፡፡ እንደ ልዋጭ። አንዱን እሴት ትቀበልና በእሱ ፋንታ ሌላውን ትሰጠዋለህ፡፡ ከልውውጡ የምታተርፈውን ነገር (እሴት) መሰብሰብ እና እንደገና በትርፍ ለመለወጥ መሞከር፡፡ ነጋዴ የመሆን ትርጉሙ በአጭሩ ይሄ ነው፡፡
የሚለወጠው ነገር የሚፈለግ መሆን አለበት፡፡ በዚህ በጨፈገገ ትውልድ ላይ እንደ ሳቅ የሚያስፈልግ ነገር የለም፡፡ ሳቅ ውስጡ የሌለው ማንም የለም፡፡ ሳቅን ፍለጋ ግን ገንዘቡን ከፍሎ “ኮሜዲ ሾ” ይገባል። ኮሜዲያን እንደ “አባ ገና” በትልቅ ስልቻ የሳቅ ገፀ በረከት ይዞ የሚዞር ይመስለዋል ታዳሚው፡፡ ግን ትልቅ ስልቻ ይቅርና ኪሱን የሚሞላ ሳቅ እንኳን ይዞ አይመጣም - እንዲያውም በተቃራኒው በኪሱ ያለው ለቅሶ ነው፡፡ እነሱ ታዳሚዎቹ በውስጣቸው ይዘው ያልመጡትን ሳቅ ኮሜዲያኑ ሊሰጣቸው አይችልም።
ኮሜዲያኑ አስማተኛ ነው፡፡ ማስመሰል ነው ስራው፡፡ ከተመልካቹ ሆድ ውስጥ ያወጣውን ሳቅ ከራሱ ሆድ ያፈለቀው አስመስሎ ማቅረብ፡፡ እኔ የገባኝ ሀሳብ ይሄ ነው፡፡ ሀሳቡን ተጠቅሜ የልዋጭ ሰራተኛ ሆንኩ፡፡ ከሰው ውስጥ የተደበቀውን ነገር ግልፅ አድርጌ መልሼ እሸጥለታለሁ፡፡ በሚስጥር፡፡
ሚስጥሩ፡- “If you don’t bring it here, you won’t find it here!” የሚል ቢሆንም፤ ሚስጥሩን ለታዳሚዬ ከገለፅኩለት አስማቴ ይነቃል፡፡ ሲነቃ፤ ጥበብ መሆኑ ይቀራል፡፡ ተራ የወሮበላ ማጭበርበር ይሆናል፡፡ መንገዱን ሳልገልፅ፤ መነሻውን እና መድረሻውን ብቻ ይፋ በማድረግ አስማቴን እሰራለሁ፡፡
መነሻው ይሄ ነው፡፡ መነሻው እንዲህ ነው። ሁሉም ሰው የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ አንዳንዱ መሳቅ ነው የሚፈልገው፤ ሌላው ማዘን፣ ሌላው ማፍቀር፣ ሌላው መክበር ወይንም መከበር … ሁሉም የሚፈልገው እና ሊያሟላው ያልቻለ አንድ ፍላጐት አለው፡፡ ያ ነው መነሻዬ፡፡ ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለው መንገድ የእኔ ሚስጢር ነው። መድረሻው ሁሉንም እንደየፍላጐታቸው መንካት መቻል ነው። መሳቅ የፈለገው ስቆ፣ ማልቀስ የፈለገው አልቅሶ፣ ማፍቀር የፈለገ ፍቅሩን አግኝቶ … ወደ ቤቱ እንዲሄድ ማድረግ፡፡ መነሻው ላይ ቃል እገባለሁ። ፍላጐቶች ሁሉ ስኬታቸውን እንደሚያገኙ፡፡ መድረሻው ላይ ብር እቀበላለሁ፡፡ ፍላጐታቸውን ከእነሱ ጋር ላገናኘሁበት፡፡
ጥበብ እና አስማተኝነት የደላላነትም ስራ ነው። ፈላጊ እና ፍላጐቱ የሚገናኙበት ምስጢር ግን ከእኔ ጋር ተደብቆ ይቆያል፡፡ የእኔ አስማተኝነት ያለው ሚስጢሩን እስከጠበቅሁ ድረስ ብቻ ነው። ከባድ የሚመስሉ ነገሮች ከብደው የሚቆዩት የክብደታቸው ምክንያት ሳይገለፅ እስከቆየበት ጊዜ ድረስ ነው። ሁሉም ሚስጢር ሲጋለጥ አስቀያሚ እና ተራ ይሆናል፡፡ የኔ ሚስጢር ደግሞ በጣም ቀላሉ ነው። መስታወት ፊት ፈላጊውን ማቆም ነው፡፡ ራሱን በመስታወቱ እየተመለከተ… ግን መመልከቱን እንዳያውቅ በእኔ አማካኝነት የራሱ ምስል ነፀብራቅ እንዲታየው አደርጋለሁ፡፡ መሳቅ የፈለገ ደንበኛዬ ራሱን በእኔ ትርጓሜ ውስጥ ያያል፡፡ ከራሱ የማንነት ምስል በላይ የሚያስቅ ነገር ምን አለ?
ማልቀስ ለፈለገውም ተመሳሳይ ነው፤ ከራስ ምስል በላይ የሚያስለቅስ ነገር ምን ይኖራል? … ግን ያጣውን ነገር ራሱ እንዳያገኝ፣ እኔ በእሱ እና የራሱ ምስል ነፀብራቅ መሀከል ቆሜ አስተረጉምለታለሁ። የራሱ ምስል በእኔ አማካኝነት ሲተረጐም ከማናደድ እስከ ማሳቅ፣ ከማሳቀቅ እስከ ማራቀቅ … ከተስፋ መቁረጥ እስከ ተስፋ ማግኘት ሊለዋወጥ ይችላል። አስማቴም ይኸው ነው፡፡ የጥበብ አስማት ሚስጢር።
ባለ ፍላጐቱ በራሱ አይን ነፀብራቁን ቢመለከት የሚያየው ፍላጐቱን እንጂ መድረሻውን አያይም። ራሱን በራሱ አይን ሲመለከት ጉድለት እንጂ ሙሉነት አይታየውም፡፡ ሁሉም ሰው ለራሱ እይታ ጉድለት ነው፡፡ እንደአጋጣሚ ሙሉ ቢሆን እንኳን ጉድለት ነው ለራሱ አይን የሚታየው፡፡ ስለዚህ አስማተኛ ያስፈልገዋል፡፡ ጉድለቱን ሞልቶ የሚነግረው። ሙሉነቱን ይዤ የምመጣው ከሌላ ቦታ አይደለም፡፡ ከራሱ ኪስ አውጥቼ ነው ወደ ፍላጐቱ የሚያደርሰውን ክፍያ የምሰጠው፡፡ ግን አስማት እንደመሆኑ፣ የሞላሁለትን ፍላጐቱን ይዞ ከትያትር ቤቱ ወጥቶ የወል ቤቱ ሲደርስ፣ ከአስማቱ በፊት ወደነበረው ማንነቱ ይመለስና ጐዶሎ ይሆናል፡፡
ሳንድሬላ በአስማተኛዋ አያቷ (አክስቷ) አማካኝነት ከአመዳም ገረድነት ወደ እፁብ ድንቅ ልዕልትነት ተቀየረች፡፡ አያቷ (አክስቷ) የከወነችው አስማት እኔ ያወራሁላችሁን ነው፡፡ ሳንድሬላን የቀየረቻት… ስለ ራሷ ያላትን አመለካከት በመቀየር ነው፡፡ ገረዲቱ በራሷ ፊት ስትቆም ይታያት የነበረውን ምስል ወደ ልዕልት ምስል ቀየረችው፡፡ ሳንድሬላ ውስጥ ቀድሞውኑ ልዕልት የመሆን ፍላጐት ወይንም ምኞት ባይኖር ኖሮ፣ በአስማተኛዋ አያቷ ሀይል ሆነ በጠንቋይ ድግምት ልትፈጠር፣ ልትለወጥ አትችልም ነበር፡፡ ፍላጐቷን እና መፍትሄዋን ከእራሷ ውስጥ አውጥታ አለበሰቻት፡፡ ከተቀዳደደ ልብሷ ውስጥ በእንቁ የተንቆጠቆጠ ቀሚስ በአስማት አማካኝነት አለበሰቻት፡፡ ከራስ ምስሏ ጋር የተቆራኙትን አይጦች፣ በነጫጭ ፈረሶች ተካችላት፡፡ ዱባውን ደግሞ ወደ ሰረገላ፡፡
በአስማተኛ አያቷ የተለወጡ ማንነቷን ይዛ ልዑላኖቹ ጋር ተቀላቀለች፡፡ ህልሟን በጥበብ አስማት እውን አድርጋ ልዑል አፈቀረች፡፡ ስድስት ሰአት ከሌሊቱ ሲሆን … አስማቱ ወደ ቀድሞው ተፈጥሮው ተቀየረ፡፡ አይጥም አይጥ፣ ዱባውም ዱባ … ሳንድሬላም ተመልሶ ተራ አመዳም ገረድ ሆነች፡፡ አስማት እና ተአምር የሚለያዩት አንዱ ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ ሌላኛው አስማት ሆኖ ይቀራል፡፡
ጥበብ የራስን ምስል ከጉድለት ወደ ሙሉነት የምትቀይር መስታወት ናት፡፡ በመስታወቷ የሚታየውን ምስል ወደ ታዳሚው ፍላጐት የሚቀይረው ሰው ጥበበኛ ይባላል፡፡ ራስን በራስ የሚቀይር ልዋጭ እንደማለት ነው፡፡ ራስን በራስ አማካኝነት የሚቀይረው ባለሞያ ጥበበኛ ተብሎ ሲጠራ መስማት የተለመደ ቢሆንም፣ ዋናው ስሙ ግን አስማተኛ ነው፡፡
የጥበብ ታዳሚው ራሱን ይዞ ወደ ትርዒቱ ስፍራ ይመጣል፡፡ በፍላጐት ተሞልቶ፡፡ የትርዒቱ ስፍራ የስዕል ሸራ፣ የመጽሐፍ ገፆች ወይንም የትያትር መድረክ ሊሆን ይችላል፡፡ ከራሱ ውስጥ ስሜቶቹን እንደ ክራር እየቃኘ … ፍላጐቱን፣ ምኞቱን ከጉድለት አውጥቶ ሙሉ ያደርገዋል - ባለ ሞያው ከተራ ቃላቶች ውስጥ ለእያንዳንዱ ታዳሚው የሚሆን መፍትሄ ያገኛል፡፡
ማልቀስ ለሚፈልገው ለቅሶ … መሳቅ ለሚፈልገው ሳቅ፡፡ የሚስቅ እና የሚያለቅሰው ታዳሚው ራሱ ቢሆንም …ሳቁና ለቅሶው ግን በራሱ ላይ ነው፡፡ በራሱ አማካኝነት ነው፡፡ በትክክል የሚገጣጥመው ጥበበኛ ካገኘ… ማንኛውም ሰው በውስጡ ሙሉነት አለ፡፡ ልዕልቷ ሳንድሬላን ትሆናለች፤ በአስማተኛው አማካኝነት፡፡ ሳንድሬላም ልዕልቷን፡፡
ግን አሁን አሁን፤ አስማተኛ የመሆን ሳይሆን አስማተኛን የማጋለጥ ፍላጐት እያደረብኝ ነው፡፡ የቆዩ የአስማት ሚስጢሮች ካልተጋለጡ አዳዲሶቹ አይፈጠሩም፡፡ ጠንከር ያሉ ወይንም ፍቻቸው ቶሎ የማይደረስበት መንገዶችን ለመፍጠር ቀላሎቹ የአስማት ሚስጢሮች “tricks” መጋለጥ አለባቸው። እውነተኛ አስማተኛ የሚለየው … ከፍላጐት ወደ ግኝቱ በሰው ስሜት መሰላል አማካኝነት ሲወጣጣ … የተወጣጣበትን መሰላል በመደበቁ አይደለም። መንገዱን እየገለፀም… ማንም መንገዱን ተከትሎ እሱ የከወነውን አስማት መስራት ሲያቅተው ነው፡፡ ሚስጢርን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን መግለፅም አዳዲስ አስማቶች እንዲፈጠሩ በይበልጥ ያግዛል፡፡
ሚስጢሩ ቢገለፅ እንኳን ማንም ማከናወን የሚችለውን አስማት እየሰሩ እውነተኛ ጥበበኛ መሆን አይቻልም፡፡ የወል የአስማት ትርዒት፣ ይትባህል እንጂ ጥበብ አይሆንም፡፡ ሚስጢሩ ቢገለጥም ማከናወን ከባድ የሆነ አስማት ሳንድሬላን አንዴ ልዕልት ካደረጋት በኋላ፣ ከሌሊቱ ስድስት ሰአት ላይ ወደ አመዳም ገረድነት (ብቃት ባለው አስማተኛ በተሰራ ጥበብ ላይ) አትለወጥም፡፡ ልዕልት እንደሆነች ትቀራለች፡፡
መለወጧ ባይቀር እንኳን፤ በሰአታት ውስጥ ሳይሆን ብዙ ዘመናት ይፈጅባታል፡፡ ለምሳሌ ዶስትዮቪስኪ እንደዛ አይነት አስማተኛ ነው የሚሉ አሉ፡፡ እኔ ደግሞ ኧ. ሄሚንግዌይ አስማቱን የሚሰራበት ሚስጢር ቢገለፅ እንኳን ማንም ሊያከናውነው የማይችል የአስማት አይነት ነው የሚሰራው ባይ ነኝ፡፡
የአስማታቸው ሚስጢር ሲጋለጥ፤ ሁሉም በየቤቱ ደብዳቤ ለመፃፍ የሚጫጭረውን ያህል ጥበብ ፈጥረው የተገኙም አሉ፡፡ ቀላሉን የአስማት ሚስጢር በማጋለጥ… ከባባዶቹ እንዲፈጠሩ መንገድ ማመቻቸት ነው… ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመርኩት ስራ፡፡ እናም እላለሁ፤ አስማተኛ አስማቱን በከረጢት ይዞ አይዞርም፡፡ አስማቱን የሚፈጥረው ከታዳሚዎቹ ፍላጐት እና ነፀብራቅ በመነሳት ነው፡፡ ታዳሚዎቹ ሀዘን፣ ደስታ፣ ተስፋ እና አንዳች ፍላጐት በውስጣቸው ቀብረው ወደ አስማተኛው ባይመጡ አስማተኛው ብቻውን የሚከውነው አንዳች ነገር ባልኖረው ነበር፡፡ If you don’t bring it here you won’t find it here! ይላችኋል፤ ጥበበኛው ባዶ ከረጢቱን እያሳየ፡፡
የአስማተኛው ጥሬ እቃዎች እናንተ ናችሁ፡፡ ጥሬ እቃዎቹን ከተራ ወደ እፁብ ድንቅነት የሚቀይርበት መንገድ ነው ሚስጥሩ፡፡ ጥበበኛ ሚስጢረኛ ነው። ምርጥ ሚስጢረኛ ግን ሚስጢሩን የሚደብቅ ሳይሆን ለመግለፅ የሚሞክር ነው፡፡ ሚስጢረኛ የሆነበትን ሚስጢር ለመፍታት በሚያደርገው ሙከራ እና ሂደት …እናንተን ከፍላጐታችሁ ወደ ግባችሁ ያደርሳችኋል፡፡ ሚስጢሩን ለመፍታት በሚሞክርበት ጊዜ ነው አስማቱ የሚፈጠረው፡፡ ከከባድ ሚስጥሮች ፍቺ የሚገኝ አስማት ነው ልዕለ - ጥበብ፡፡ የልዕለ ጠቢብም አሻራ:- ሚስጥርን መግለፅ እንጂ መደበቅ አይደለም፡፡ በተገለፀ ቁጥር የሚደበቅ ሚስጥርን ለመፍታት ጠንካራ አስማተኞች ያስፈልጉናል፡፡ እውነተኛ አስማተኞች፡፡ ካርታን ደርድሮ “ቀዩዋን ያየ” እያሉ የሚያጭበረብሩት…እውነተኛም፣ ሚስጥረኛም አስተማኛም አይደሉም። ምናልባት “ወሮበላ” ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግልፁን ሚስጢር የሚያደርግ እና ሚስጢሩን ለመግለፅ በሚሞክር መሀል የሰማይ እና የምድር ያህል ርቀት አለ፡፡ አንደኛው ወሮ በላ ይባላል፡፡ ሌላኛው አስማተኛ ነው፡፡ አስማተኝነትን ከሌላ አስማተኛ በመማር ሚስጢሮችን እና አፈታታቸውን አጥንቶ፣ “የጥበቡ ጥሪ አለኝ” የሚል ሊጀምር ይችላል፡፡
አዲስ አስማት መፍጠር ካልቻለ … ወይንም ካልሞከረ ግን በስተመጨረሻ የሚገባው ወደ ማጭበርበሩ ነው፡፡ ቀላልን ሚስጢር ከባድ አስመስሎ ወደመደበቁ፡፡


Published in ጥበብ
Monday, 18 November 2013 11:34

እሳቱ

                       በባህል አብዮቱ ወቅት፤ ቀይ ቃፊሮቹ፤ በየደረሱበት ያገኙትን ማናቸውንም አይነት ምስሎች እየሸረካከቱ፣ እየቦጫጨቁ ይጥሉ ጀመር፡፡ ከሊቀመንበር ማኦ ምስል በቀር፡፡ የሀገረ ቻይናን ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሳ ቅርሶች ሁሉ እንክትክት አድርገው እየሰባበሩ ዱቄት አደረጉት፡፡ አንድም የመጽሀፍ ዘር የተባለ ሳይቀራቸው፤ ከያለበት ሰብስበው በማውጣት እሳት ለቀቁበት፡፡ ከሊቀመንበር ማኦ መጻሕፍት በቀር፡፡
በተቃዋሚ ጎራ የተፈረጁ ቤተሰቦች ዕጣ ፈንታ እጅግ መራር ነበር፡፡ ቀይ ቃፊሮቹ፤ ድንገት በራቸውን በርግደው ይገቡና ጓዳ ጎድጓዳቸውን ይበረብራሉ፤ የቤት እቃዎቻቸውን፡- ብስክሌት፣ የግርግዳ ሰአት፣ ጥሩ ጥሩ ልብሶችንና የህፃናት መጫወቻዎችንም ሳይቀር፤ ዋጋ ያወጣልናል ብለው የገመቱትን ነገር ሁሉ እየሰበሰቡ ይወስዳሉ። የማይፈልጉትን እንኳን አይተዉትም፤ ወደ ውጪ እየወረወሩ ከስክሰው ያደቅቁታል እንጂ፡፡ በቤተሰቡ አባላትም ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ ይፈጽማሉ፡፡ አንዳንድ ልጃገረዶች፤በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ያረገቡ መስሏቸው ለአብዮተኞቹና ጭፍሮቻቸው ክቡር ገላቸውን አበርክተዋል፡፡
በመንደሩ ውስጥ የሚኖሩ ድሃ ጭሰኞች፣ የበኩር ልጅ የሆነ አንድ መልከ ጥፉ ጎረምሳ ነበረ። ዕድሜው ከሰላሳዎቹ ቢዘልልም ሰነፍ፣ ዘልዛላና ጅላጅል ቢጤ ስለሆነ ትዳር ያልያዘ ‹‹ቆሞ ቀር›› ነው። “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንዲሉ፤ በሀገሬው የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ምስቅልቅል እንደጥሩ አጋጣሚ ቆጥሮ፣ በአንድ እጁ ማስፈራሪያ፣ መሸንቆጫ ጉማሬ አለንጋውን፤ በሌላ እጁ ቡትሌውን ጨብጦ፤ አዛዥ ናዛዥ ሆኖ ቁጭ አለ። ሀይ ባይ አጣ፡፡ በአሳቻ ሰአት ወጣት ልጃገረዶች ባሉበት የተቃዋሚ ቤተሰቦች ቤት እንዳሻው ዘው እያለ፤እምቡጥ ኮረዳዎቹን እያርበደበደ፤ እምቢኝ ብለው ሲተናነቁት እጃቸውን ጠምዝዞ ገፍትሮ በመጣል ጉልበት ከድቷቸው በወደቁበት ጨምድዶ ይዟቸው፤ አይናቸውን እያቁለጨለጩ ሲንፈራገጡ፤ይበልጥ ትንፋሽ አሳጥቶ ጉሮሯቸውን አንቆ በመያዝ፤ ልብሳቸውን እየሸነታተረ፤ አስገድዶ ይደፍራቸዋል፤ በእንባ እየታጠቡ፡፡
አቶ ሻንግ ደግሞ፤ ዕድሜያቸው ከስድሳው የገፋ፤ በሰዎች ዘንድ በፀባይና ምግባራቸው የተከበሩ አዛውንት ናቸው፡፡ አብዛኛውን ዘመናቸውንም ያሳለፉት የባለጸጋ ነጋዴዎችንና የባለስልጣን ቤተሰቦች ልጆችን፤ ቱባውን የቻይና ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን፣ የኪነ ጥበባት፣ ኃይማኖታዊ ፍልስፍና … ትውፊታዊ አንድምታዎችን እውቀት በማስተማር ነው፡፡
ከሦስት ትውልዳቸው ጀምሮ በቅብብሎሽ የመጣውን ጥንታዊውን ዕምቅ ጥበብ ስለወረሱም፤ በጥልቅ ልቦና የተፀነሱ በርካታ የፈጠራ ስራዎችን አምጠው የወለዱ፤ ሰማየ ሰማያት የመጠቁ ረቂቅ ቅኔዎችን ስንኝ የሰደሩ… እንዲሁም ልዩ ግንዛቤ እሚሻውን የቻይናን የፊደል አፃፃፍና ትርጓሜ (ካሊግራፊ) ክህሎት ያካበቱ ‹‹አራት አይና›› ልሂቅ ናቸው፡፡ ይኸውም አፍ በእጅ የሚያሲዝ አድናቆትን የተናኘ ጉምቱ ስብዕናቸው፤ ከሚኖሩበት መንደር አልፎ በሌሎቹም አጎራባች ከተሞች ሁሉ፤ እንደ ብርቅ የሚታዩ ስመ ጥር ሰው አድርጓቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ዝናቸውን ያገነነው ግን ያሏቸው የመጻሕፍት ብዛት ነው፡፡
ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው ጀምሮ፤ ቤተሰቦቻቸው ሁሉ ከፍተኛ የንባብ ፍቅር ያደረባቸው ነበሩ፡፡ የርሳቸው የመጽሀፍ ቁርኝት ደግሞ እብድ ሊያሰኛቸው የሚያደርስ ነው። ከሚያገኙት ገቢ አብዛኛውን ለመጻሕፍት መግዣ ያውላሉ፡፡ እንዲያውም፤ አንዳንድ ሰዎች፤ ‹ለመጽሀፍ መግዣ ያወጡትን ገንዘብ… እርሻ ቢያስፋፉበት ኖሮ፤ እንዴት ያሉ የመሬት ከበርቴ መሆን በቻሉ ነበር!› ይሏቸዋል፡፡ በመጻሕፍት ስብስቦቻቸው አይነት፤ በሰሜን ቻይና ውስጥ አቻ አይገኝላቸውም። በቁጥር ከሦስት ሺህ በላይ መጻሕፍት አሏቸው፡፡ አንዳንዶቹ በዋጋ የማይተመኑና በሚንግ ና ሶንግ ዘመን (ከአምስት እስከ ስምንት መቶ አመታት በፊት) የተደጎሱ ናቸው፡፡ አቶ ሻንግ፤ በደብሊው ከተማ በተካሄደው የፖለቲካ ምክክር መድረክ ላይ፤ በክብር አባልነት ተጋብዘው የተሳተፉበት ጊዜም ነበር፡፡
ከ1949ኙ ለውጥ በኋላ ግን አቶ ሻንግ፤ ወደ ቀድሞው የመምህርነት ሞያ አልተመለሱም፡፡ ወደ ትውልድ መንደራቸው አቅንተው በጭሰኝነት መተዳደር ጀመሩ፡፡ ስለ ግብርና መጠነኛ ዕውቀት ስለነበራቸው፤ የመንደሩ ነዋሪዎች መልካም አቀባበል ነበር ያደረጉላቸው፡፡ አዛውንቱ ፤ አስተዋይ፣ ታማኝና ግብረገብ አዋቂ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ የአዲስ አመት ብስራት መግለጫዎችን፣ በመንደሪቱ ውስጥ ለሚደገሱ የሠርግ በዐላት የሚሆኑ መጥሪያዎችን በማዘጋጀት፣ ስዕሎችን በመሳልና ግጥሞችን በመፃፍም ስለሚተባበሩ፤ በነዋሪዎቹ ዘንድ ተወዳጅ ሰው ሆኑ፡፡ እናም፤ እንደ አንድ ምስኪን ጭሰኛ ተረጋግተው በሚመሩት ሰላማዊ የገጠር ህይወት፤ ከፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ጦስ ሉተርፉ ችለዋል፡፡
የግርግሩ ወቅት ግን፤ እገሌ ከእገሌ፣ ትንሽ ትልቅ ሳይል፤ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላሉት ሆነ በጭሰኝነት ለሚንገታገቱት ድሆች ሳይቀር እረፍት የሚነሳ አስከፊ ጊዜ ሆነ፡፡ ዜጎች፤ በየጣራቸው ስር የሚገኙ መጻሕፍቶቻቸውን አንዲትም ሳያስቀሩ መቀዳደድ ወይም ማቃጠልና ይህንኑም ድርጊታቸውን በየመንደሮቻቸው ታጥቀው ለሚንጎማለሉት የቀይ ቃፊሮቹ ጭፍሮች አሊያም ለአዛዥ ካድሬዎቻቸው ያሉበት ድረስ ሄደው የማሳወቅ ግዴታ ተጥሎባቸው ነበር፡፡ አዬ የቀን ጎዶሎ! እንግዲህ የአቶ ሻንግ መጻሕፍት ዕጣቸው ምን ይሆን? አዛውንቱ ያሉዋቸው መጻሕፍት ከሦስት ሺህ በላይ ስለሆኑ፤ እንዲህ በቀላሉ ካንዱ ስርቻ የሚሸጎጡ፣ ወይም አንዱጋ የሚደረጉ አይደሉም - መቸም፡፡ አቶ ሻንግ ደግሞ፤ መጻሕፍታቸው፤ በሌላ ማንም ባዕድ እጅ ንክች እንዲደረግባቸው ከቶም አይሹም፡፡ ምን ሲደረግ! ‹‹መፅሀፍቶቼ ለእኔ ህይወቴ ናቸው!›› ይላሉ፡፡
የዛን እለት ግን አይቀሬው መከራ እውን ሆነ፡፡ የሆነው ሁሉ የሆነው… እሳቸው በሌሉበት ነበር፡፡
ሚስታቸው፤ መቼም ይሁን መች፤ ያው የእነርሱም ተራ ሲደርስ፤ በድንገት መዝጊያቸው በሀይል ተከፍቶ፤ ቤታቸው እንደሚበረበር ታውቅ ነበርና፤ አዛውንቱ፤ አይናቸው ሥር መጻሕፍቶቻቸው ሲቃጠሉ እንዳያዩ ስትል፤ራቅ ያለ ስፍራ የሚኖሩ ዘመዶቻቸውን ጠይቀው እንዲመጡ አግባብታ ሸኘቻቸው፡፡ ወዲያውም፣ ጊዜ ሳታጠፋ፣ በርራ በመንደሩ ወደሚያንዣብቡት ቀይ ቃፊሮች ዘንድ ሄዳ፤ እጅ መንሳት፤ ባለቤቷ አቶ ሻንግ በሌሉበት፤ አሁኑኑ በፍጥነት መጥተው፤ መጻሕፍቶቹን ከቤት በመውሰድ ውለታ እንዲውሉላት ተማፀነቻቸው፡፡
መጻሕፍቱ፤ ተለቃቅመው ተወስደው ዋና ከተማ ሲደርሱ፤ ቀይ ቃፊሮቹ ባስመዘገቡት ታላቅ ስኬት፣ ከአዛዦቻቸው ሙገሳና ውዳሴ ተዥጎደጎደላቸው። ምክንያቱም፤ እስከዛሬ ከዜጎች ታዛ ወጥተው ከታዩት መጻሕፍት ሁሉ በብዛት በመብለጣቸውና ከመጻሕፍቱ ጋርም፤ አዛውንቱ እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ሲጠበቡባቸው የኖሩት ሁለገብ የጥናትና ምርምር ዶሴዎች፤ ውብ የፈጠራ ድርሰቶች፣ በርካታ ያለቁ የስዕል ቅቦች፣ በእንጥልጥል ያሉ ያልተቋጩ ስራዎች፣ አዳዲስ ጅምር ንድፎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ቅኔዎች ጥራዞችም አብረው ተጭነው ነበር፡፡ አብዮተኞቹ አደልበው ለሚመገቧቸው አሳማዎች የሦስት ቀን መኖ በመሆን፤ የተረፈውም ለምግብ ማብሰያ ማገዶነት ውሎ ባለስልጣናቱን ከቀለብ ወጪ አድኗቸዋል፡፡
አቶ ሻንግ፤ ዘመድ ጥየቃ ከሄዱበት ተመልሰው የሆነውን ነገር ሁሉ በሰሙ ጊዜ፤ ራሳቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው መሬት ላይ ተዘረሩ፡፡ ልጆቻቸው፤ አፋፍሰው ተሸክመው፤ ወደ ቤት አስገቧቸው፡፡ አልጋ ላይ አስተኟቸውና ሀኪም በቶሎ መጥቶ እንዲያያቸው አደረጉ፡፡
ከሳምንት በኋላ፤ አዛውንቱ ከህመማቸው ቢያገግሙም፣ በዕድሜያቸው ላይ አስር አመታት ያህል የጨመሩ መስለው፤ እርጅት ብለው ታዩ፡፡ ቀኑን ሙሉ፤ ተጠራርገው የተወሰዱት መጻሕፍቶቻቸው ለዘመናት በክብር የኖሩበትን፤ እራቁቱን የቀረ ባዶ መደርደሪያ፤ ትክ! ብለው እያዩ፤ በፅናት ሲሰበስቧቸው የኖሩት የመጻሕፍት አይነት ድቅን ሲሉባቸው፤ ተንሰቅስቀው ያነባሉ፡፡
እነዚያ እፁብ ድንቅ መጻሕፍት የተደራጁት፤ ከቅድመ አያታቸው ዘመን ጀምሮ እስከ ሦስት ተከታታይ ትውልድ የቤተሰቦቻቸው ውርስ ነበሩ። እርሳቸውም በተራቸው እየገዙ፤ ላባቸውን ጠብ አድርገው፣ ደም ተፍተው ሰርተው ከሚያገኟት ገቢ ላይ እየቆጠቡና ላደረባቸው የንባብ ፍቅር ተሸንፈው፤ ጦም እያደሩም ጭምር ነበር ያጠራቀሟቸው፡፡
‹‹እኮ መፅሀፎቼ ምን በደሉ? አምላኬ ሆይ!›› እያሉ ያለቅሳሉ፡፡ ግን ደግሞ፤ በድብቅ እንጂ፤ ፊት ለፊት ሀዘንን መግለፅ በአብዮቱ የተከለከለ ነው! ቤትን ዘግቶ መነፋረቅ ይቻላል!!! ነው ህጉ፡፡ ባለቤታቸው፤ ሀዘናቸውን እንዲረሱ የምትችለውን ሁሉ ብትጥርም ከንቱ ድካም ሆነባት፡፡ አዛውንቱ፤ ለአምሳያ ታሪክ ትዝብታቸው እንዲህ ሲሉ ስንኝ ቋጥሩ...
ሺህ መጻሕፍት ተቃጥለው
ጢሱ ነክቶ ሰማይ፤
ንጉሠ ነገስት ቺን
አይን ኖረው እሚያይ፡፡
(ንጉሠ ነገስት ቺን፤ በፈላጭ ቆራጭ አገዛዙ የታወቀ፣ ከሁለት ሺህ ሁለት መቶ አመታት በፊት በነበረው የንግሥና ዘመኑ፤ የትየለሌ መጻሕፍትን በማቃጠሉና አምስት መቶ ያህል ልሂቃን ዜጎችን በመፍጀቱ የሚታወቅ ግፈኛ ንጉሥ ነበር፡፡)
ሊቀመንበር ማኦ እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹ከእኛ ጋ ሲነፃፀር፤ ንጉሠ ነገስት ቺን ምንም ነበር፤ እኛ በቁርጠኛው አመራራችን፤ በልሂቃን ነን ባይ ዜጎቻችን ላይ የወሰድነው የማያዳግም ቆራጥ እርምጃ፤ ከእሱ መቶ እጥፍ የሚያስከነዳ ነዋ!››
እጅግ ብርቅና ውድ የሆኑ ቅርሶች ሁሉ እሳት ተማገዱ፡፡ መጻሕፍት,፣ ረቂቅ የስዕል ጥበብ ውጤቶች፤ቤተሰቦች ከጥንት በውርስ የተላለፈላቸውና ለረዥም ዘመናት በክብር የያዙዋቸው የትውልዳቸው የዘር ሀረግ መጠበቂያ መዛግብት፤ እናም አሮጊቶች ከልጃገረድነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ከየቁምሳጥኖቻቸው አናት ላይ በልዩ ሙዳየ ሳጥን ከፍ አድርገው ሰቅለው,፣ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በትዝታው እየታደሱ በስስት ያቆዩዋቸው፡ ለማይደገመው የሠርግ ቀናቸው የለበሷቸው ውብና ደማማቅ አልባሳት ሁሉ፡፡
የተቃዋሚ ጎራ አባላቱና ቤተሰቦቻቸው፤ ገና ለአካለ መጠን ያልደረሱ እምቦቃቅላ ልጆቻቸውን ጭምር ይዘው፤ በእሳቱ ዙሪያ እንዲሰባሰቡ፤ ከዚያም ፊት ለፊታቸው የሚንቀለቀለውን ነበልባል ከብበው፣ በደንብ ጥስቅ አድርጎ እንዲቆረቁራቸው ታስቦበት ኮረት በተነሰነሰበት ጉርብጥብጥ መሬት ላይ፤ ልብሳቸውን ወደ ባታቸው እየሰበሰቡ,፣ በሌጣው ጉልበታቸው እንዲንበረከኩ ተገደዱ፡፡
ቀይ ቃፊሮቹ፤ ከኋላቸው ዙሪያቸውን እየተሯሯጡና በቁጣ እያምባረቁባቸው፤ እጃቸው የገባውንም አፈፍ አርገው እያምቸለቸሉ ያሰቃዩዋቸዋል፡፡ ጀርባቸውን ይዠልጧቸዋል። ሴቶቹን በፀጉራቸው መሬት ለመሬት እየጎተቱና ዞማቸውን ቆዳቸው ስር ገብተው እየመደመዱ፤ በአናታቸው አመድና ትቢያ ይነሰንሱባቸዋል፡፡
በድንገት፤ አንዱ ጠብደል ቀይ ቃፊር፤ ‹‹ጩኹ!›› የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ከዚያም እየፎከረ,፣ እየፎገራ፤ ‹‹እናንተ ጭራቅና ሰይጣኖች ናችሁ! እኛ አብዮት ነው ያቀጣጠልነው፤ የአብዮታችን ወጋገን ደግሞ፤ ነበልባሏ አራስ ልጅም ልትበላ ትችላለች! እህ ምን ታመጣላችሁ እሺ?! በሉ‚ኮ ለእነርሱ አልቅሱላቸው! ለአብዮታችን ለምንሰዋቸው ጨቅላዎች!እ?! አልቅሱኮ ነው የምለው!! በሉኮ አልቅሱ!!!›› እያለና አስሩን እየዘላበደ፡ እየደነፋ፣ እያቅራራ፤ በያዘው አንጀት የሚያሳርር ብረት አለንጋ ያለ ርህራሄ ይነርታቸው ጀመር። ከመሀከላቸው፤ ስቃዩን መቋቋም ያቃታቸው፤ ራሳቸውን መርዳት የማይችሉ አቅመ ደካሞች፤ ጉልበታቸው እየተብረከረከ ወደሚግለበለበው እሳት ወደቁ፡፡ ከመላ አካላቸው ሁሉ በፊት፤ ፀጉርና የአይን ሽፋሽፍቶቻቸው በነበልባሉ ሲንጨረጨሩ፣ ሽታው አካባቢውን ያቆንሰዋል፡፡
አንዲት ለጋ ቀምበጥ፤ በእድሜ የገፉትን የምስኪን እናትና አባቷን ሰቆቃ ማየት ከአቅሟ በላይ ሆኖባት፣ ድምጿን ከፍ አድርጋ ‹‹እኔን ግደሉኝ! ቤተሰቦቼን ተዉአቸው! እባካችሁ ልለምናችሁ?! በእነሱ ፈንታ ይኸው እኔን ግደሉኝ?!›› አለች፡፡ ግን ማንም ጉዳዬ ያላት አልነበረም፡፡ ወዲያውም ራሷን ወደ እሳቱ ወረወረች፡፡ ሙሉ ለሙሉ የወደቀችበት እሳት በቅፅበት ከፀጉርና ሽፋሽፍቷ ጀምሮ ልብሶቿን እያያያዘና እያቀጣጠለ አገነተራት፡፡ ሁለት ደጋግ ሰዎች፤ ጎትተው ወደ ዳር አወጧት፡፡ ሆኖም ግን እሳቱ መላ አካሏን ፈጅቶ በልቷታል፡፡ አንድም ያልተቃጠለ የሰውነት ክፍል አልነበራትም፡፡ በተለይ ፊቷ ክፉኛ በመጎዳቱ፤ መልኳን አይቶ ለመለየት አስቸጋሪ ነበር። ስምንቱ የእጅ ጣቶቿም ተጎርደው ስለወደቁ፤ በቀድሞ ቦታቸው ላይ ምልክታቸው ብቻ ቀረ፡፡
ይህቺ መከረኛ ውብ ወጣት፤ምንም በማታውቀው ጉዳይ፤ ‹‹ያለፈው ስርአት ርዝራዦች ዲቃላ!›› በሚል ነው በተቃዋሚነት የተኮነነችው፡፡ የሀኪም እርዳታ ማግኘት የሚታሰብ አልነበረምና፤ ለረዥም ጊዜ ሳትገላበጥ በአንድ ጎኗ ብቻ በተኛችበት ደንዝዛ ከረመች፡፡ ቆይቶም ዘመዶቿ፤ በእሳት ነፍሮ የተወለጫጨመ ሰውነቷን አጣጥበው ሲያበቁ፤ ባህላዊ መድኃኒት ነው ያሉትን ቅጠል ጨምቀው አሻሹላት፡፡
ሆኖም ግን፤ የደረሰባት ቃጠሎ፤ በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ስላላገኘ፤ ፊቷ የቋጠረው ደምና መግል እያደር እያዠ፣ እያመረቀዘ፤ ፍፁም ሌላ አይነት አስፈሪ ግን ደግሞ አንጀት የሚያላውስ አሳዛኝ አይነት ገፅታ ይፈጥር ጀመር፡፡ በእቶኑ ስለት ተቆርጥመው የተጎነደሹ ውብ ጣቶቿ ተተክለውባቸው የነበሩት፤ በእሳቱ ረመጥ ነፍረው፣ አርረው የከሰሉት የእጅ መዳፎቿም፤ ፈጽሞ መንቀሳቀስ የማይችሉ፤ በድን ሆነው ቀሩ፡፡
ምንጭ - (Australian Short Stories No.58 -1997. THE FIRE Shi Pang Fan.)

ከሦስት ትውልዳቸው ጀምሮ በቅብብሎሽ የመጣውን ጥንታዊውን ዕምቅ ጥበብ ስለወረሱም፤ በጥልቅ ልቦና የተፀነሱ በርካታ የፈጠራ ስራዎችን አምጠው የወለዱ፤ ሰማየ ሰማያት የመጠቁ ረቂቅ ቅኔዎችን ስንኝ የሰደሩ… እንዲሁም ልዩ ግንዛቤ እሚሻውን የቻይናን የፊደል አፃፃፍና ትርጓሜ (ካሊግራፊ) ክህሎት ያካበቱ ‹‹አራት አይና›› ልሂቅ ናቸው፡፡ ይኸውም አፍ በእጅ የሚያሲዝ አድናቆትን የተናኘ ጉምቱ ስብዕናቸው፤ ከሚኖሩበት መንደር አልፎ በሌሎቹም አጎራባች ከተሞች ሁሉ፤ እንደ ብርቅ የሚታዩ ስመ ጥር ሰው አድርጓቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ዝናቸውን ያገነነው ግን ያሏቸው የመጻሕፍት ብዛት ነው፡፡

Published in ልብ-ወለድ

               በ17ኛው ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ ገኖ የወጣ አፍቃሬ−አመክንዮ ፈላስፋ ነው፤ ዴካርት። በአለም የፍልስፍና ታሪክ ውስጥም የዘመናዊ ፍልስፍና አባት ተደርጎ ይቆጠራል። የነባሩን የፍልስፍና ባህል እና የዘመኑን የሳይንስ አባዜ አጣምሮ ወጥ ስራ በመስራት ዘመኑን አስደንቋል። የምዕራቡን (የአውሮፓን) ዳግም መነሳሳት ካቀነቀኑት መካከል የሚጠቀሰው የታላቁ ሠዓሊ ሊዮናርዶ ዳቪንቺ እያንዳንዷ የሐሳብ ቅንጣት ከሬኔ ዴካርት ሐሳቦች ጋር ተመሳሳይ እንደሆኑ ይገመታል። በሒሳብ ባለሙያነቱ የሚታወቀው ሬኔ ዴካርት፤ ፍልስፍና በዘመናዊ የሳይንሳዊ ዘዴ እንድትመራ ፈር ቀዳጅ ፈላስፋ ለመሆን በቅቷል። የፍልስፍና ዘዴው በተለየ ሁኔታ የካርቴዚያን ፍልስፍና ተብሎ ተሰይሞለታል። የሒሳብ ቀመሮቹም ካርቴዚያን ማቲማቲክስ እየተባሉ እንደሚጠሩለት ማለት ነው። አናሊቲካል ጂኦሜትሪ እና አናቶሚካል ኤክስፐርመንቶች ላይ ከፍተኛ ስራ እንደሰራ የሚነገርለት ዴካርት፤ የጋሊሊዮ ቀንደኛ አድናቂ ነበር ይነገራል።
ለዴካርት ፍልስፍና ማለት “የጥበብ ጥናት” ማለት ነው፤ “ማንኛውም ሰው ሊያውቀው የሚችል ፍጹም እውቀት የፍልስፍና አገልግሎቶቹ/ጥቅሞቹም ስለ ሕይወት አኗኗር (ሞራል) ስለጤና አጠባበቅ (ህክምና) እና ስለሙያ ፈጠራ (ክህሎት/መካኒክስ) ማወቅ ነው ይላል። ይህንን ሐሳቡን በተምሳሌት ሲያስረዳም “አንድን ዛፍ ብንወስድ ስር፣ግንድና ቅርንጫፍ አለው። ስሩ ኅላዌን ሲወክል፤ ግንዱ ቁስ/ግዑዝ አካላትን ይወክላል፤ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ሞራል፣ህክምና እና ክህሎት ናቸው።” ይለናል። የዛፍ ስሩ ጥልቅ ነው፤ ወደ ውስጥ መሬትን ቆንጥጦ በመያዝ ምግብና ውኃ በማቅረብ ስለሚያገለግለው የዛፉ ኅልውና እንደመሆኑ ሁሉ የፍልስፍና መሰረትም ኅላዌ/ዲበ አካል (metaphysics) ነው። ሌሎች የፍልስፍና ዘርፎችን የዲበ አካል ጥገኞች ያደርጋቸዋል፤ እንደ ዛፉ ግንድና ቅርንጫፍ ማለት ነው።
የሬኔ ዴካርት የዲበ አካል/ኅላዌ ፍልስፍና ከእርሱ ቀደም ብሎ እንደ መጣው ፍራንሲስ ቤከን፤ በስሜት ህዋሳትና በይሆናል ሳይሆን በሒሳብ ስሌት ላይ በመተማመን በእርግጠኝነት ላይ እንዲመሰረትለት ጥሯል። “ከፊት ለፊቴ እሳት ይነዳል፤ የሌሊት ካፖርት ለብሻለሁ፤ ጠረጴዛዬ ላይ ወረቀትና ብዕር ይታየኛል……ነገር ግን እነዚህ ሁሉ እውነት ስለመሆናቸው ምን እርግጠኛ የሚያደርገኝ ነገር አለ? ከዚህ በፊትም ብዙ ነገሮች በእውነት የተከናወኑ መስሎኝ ነገር ግን በህልሜ የሆኑ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ዛሬስ በህልሜ ላለመሆኑ ምን እርግጠኛ የሚያደርገኝ ነገር አለ? እንዲህ እያለ ነው ዴካርት “ተመስጦውን”/ፍልስፍናውን የሚጀምረው። የ”ጥርጣሬን” መንፈስ በልቦናው ያነግሳታል። ሁሉንም ነገር፤ የሚያየውን፣የሚዳስሰውን፣የሚያሸተውን፣ የሚቀምሰውን በአጠቃላይ በስሜት ህዋሳቱ አማካኝነት የሚያገኘውን መረጃ በሙሉ ከመቀበል ይልቅ በጥያቄና በጥርጣሬ ያዋክባቸዋል። አውሮፓ ድንበሯ እየተለጠጠ ሳይንስና አዳዲስ ግኝቶች እየተስፋፉ እንዲሁም አዳዲስ የዓለም ክፍሎችን እየተዋወቁ የመጡበት ዘመን ስለነበር፤ እውቀት ለሰው ልጅ የሚቻል ነገር አይደለም የሚለውን የቀደመ አስተሳሰብ ለመስበር ታትሯል።
እርግጠኛ የሆነ እውቀትን ለማግኘት ዴካርት የተጠቀመበት ዘዴ ደግሞ፤ ከዚህ በፊት እርግጠኛ የሆንባቸውን ነገሮች ሁሉ በመጠራጠር እና ባለመቀበል ነው። እናውቀዋለን የምንለውን ነገር ሁሉ በጥያቄ ማብጠርጠር ማለት ነው።” ዘላቂና የማይናወጥ እውቀትን መመስረት ካለብኝ፣ እስከዛሬ በሕይወት ዘመኔ የሰበሰብኩትን እውቀት ተብዬ ሁሉ ድምጥማጡን ማጥፋት እንዳለብኝ ተገንዝቤአለሁ” ይለናል፤ “ቀዳማዊ ተመስጦ” በተባለው ድርሳኑ በአካባቢያችን ያሉ ነገሮችን ሁሉ እየበረቃቀስን እና እያብጠረጠርን መፈተሽ እንዳለብን ያሳስባል፤ ዴካርት።ይህንንም ተከትሎ ሦስት አፈንጋጭ ሙግቶችን ያቀርባል፤ በዘልማድ የተቀበላቸውን ነገሮች ሁሉ ለማስወገድ እንዲረዱትና እርግጠኛ የሆነ እውቀት ለመመስረት እንዲችል። እያንዳንዱን እምነቱን አንድ በአንድ በመጨፍለቅ ሳይሆን መሰረታዊ የእምነቱን መርሆዎችን ማንገራገጭ እንደ ስልት ይጠቀማል፤ ዴካርት። በመሰረታዊነት የተጠቀመባቸውን ሦስቱን ሙግቶች እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።
ሀ) ማንኛውንም ያልተመረመረ ሐሳብ እና በስምምነት የተቀበልነውን ሁሉ በተደራጀና መመሪያዎችን በተከተለ መልኩ በጥርጣሬ መፈተሽ። ወይም ባጭሩ አፈንጋጭነት ልንለው እንችላለን። ይህ በየዋህነት የተቀበልናቸውን አስተሳሰቦች ለማጥቃት የተጠቀመበት ሙግት ነው። “ከጊዜ ወደ ጊዜ የስሜት ህዋሶቼ እያጭበረበሩኝ እንደ ሆነ ደርሸበታለሁ።” የሚለው ዴካርት፤ “ለአንዲት ጊዜ እንኳን ያታለለችኝን የስሜት ህዋሴን አለማመኔ ሁነኛ እርምጃ ነው” ይላል።
ለ) ያልጠራ፣ እራሱን ያልቻለ እና ግጭቶች/መፋለሶች ያሉበትን ሐሳብ አለመቀበል። The Dream Argument (የህልም ሙግት) እየተባለ ይጠራል፤ ሁለተኛው የዴካርት ሙግት።
ሐ) እራስን በማወቅ፤ ከዓለት በጠነከረ መሰረት ላይ ሐሳባችንን መስርተን፤ በማንኛውም ጥርጣሬ የማይነዋወጥ ከራስ ከውስጥ የመነጨ “እያሰብኩ ስለሆነ እኔ ኅልው ነኝ” የሚል ግለሰባዊነት ላይ መድረስ። (“Cogito, ergo sum”)
“የስሜት ህዋሳት አንዳንዴ ያጭበረብሩናል። ባለ ጠርዙን ማማ ከሩቅ ስናየው ድቡልቡል አድርገው ያሳየናል፤ ቀጥ ያለ እንጨት ውኃ ውስጥ ብንከትተው ስብርብር ያለ ሆኖ ይታዩናል፤ ስለዚህ የስሜት ህዋሳት የሚታመን ብያኔ አይሰጡንም ማለት ነው። አንዳንዴ ደግሞ ህልምና እውኑን መለየት ይቸግራል፤ “አልጋው ላይ እንዳልተጋደመ ሰው ሁሉ ጥርት ያሉ ምስሎችን አያለሁ፤ በህልሜ መሆኑን እንኳን የምለይበት ምንም ምልክት አጣለሁ” ዴካርት ይህንን እያምሰለሰለ ይቀጥልና እንዲህ ይለናል። “በስሜት ህዋሳቶቼ የማገኘውን መልእክት ባልቀበልም ይኸው ደግሞ ሌላ እውነት የሚመስል ነገር የሚያሳውቀኝ ሌላ መንገድ አለ።” የህልሙን እና የስሜት ህዋሳቱን መልእክት ይበልጥ እያፍተለተለ ከፍ ወዳለ ሃሳብ ይወሰደዋል። “የሚያታልለኝ ኃይል አለ ማለት ነው።ፈጣሪ ይህንን ሊያደርግብኝ ይችላልን? ይህንን ካደረገብኝማ “ፍጽምና” ባህሪው ሊሆን አይችልም። ስለዚህ እኔን ለማወናበድ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ የሚሰራ ሌላ አወናባጅ ዲያብሎስ አለ ማለት ነው” ይላል ዴካርት።
ስለዚህም የዚህን አወናባጅ ዲያብሎስ ምክር ለማሸነፍ ሐሳቦቸን ግልጽ፣ ልዩ (እራሱን የቻለ) እና እርስ በርሱ የማይፋለስ በማድረግ ወደ ፍጹማዊው የፈጣሪ ባህሪ ማስጠጋት አለብን ማለት ነው። ሐሳባችንን በዚህ ቀመር ማስላት ከቻልን፣ በንጹህ ልቦናችን ፈጣሪ እውነትን ስለሚለግሰን ለምናስበው ነገር እርግጠኛ መሆን ይቻለናል ማለት ነው።
በዚህ የሒሳብ ቀመራዊ አስተሳሰብ እየተመራን የማንጠራጠረው እውቀት ካገኘንና ጥያቄዎቻችንን ሁሉ መመለስ ከቻልን የእራስ ኅልውና አገኘን ማለት ነው። በአካባቢያችን ያሉትን ሁሉንም እየተጠራጠርንና እየጠየቅን በቀላሉ ስለ ህልውናቸው እርግጠኛ መሆን አንችልም፤ ነገር ግን አንድ መካድና መጠራጠር የማልችለው እውነት አለ፤ ይኸውም በአሁኑ ሰዓት እያሰብኩ መሆኑን ልቦናዬ እየነገረኝ ነው።
“እያሰብኩ ስለሆነ ኅልው ነኝ ማለት ነው” ይለናል ዴካርት። ሁሉንም የቀደሙ እውቀቶችን እንዲፈትሻቸው የነገረው አንድ እርግጠኛ የሆነ ሳይንሳዊ እውቀት ፍለጋ ሲሆን፤ አንድ እርግጠኛ እውነት ካገኘ ሙሉ ፍልስፍና አድርጎ ሥጋና ደም እንደሚሰጠው እርግጠኛ ነበረ፤ ዴካርት። ስለሆነም አሁን ልቦናው የሚነግረው እርግጠኛ እውቀት እያሰበ መሆኑን ሆኖ አገኘው። እኔ ግን ምንድን ነኝ? ይላል እንደገና። የሚያስብ ቁስ ነኝ ማለት ነው። አዎን እያሰብኩ መሆኔን መካድ ስለማልችል፤ እኔ የማስብ ነገር ነኝ ማለት ነው። የማስበው በአእምሮዬ ነው፤ አእምሮ ደግሞ ግዙፍ አካል የለውም። ረቂቅ ነገር ነው፤ ስለሆነም አይበሰብስም፣ አይፈረከስም፣ አይሞትም ማለት ነው። ሆኖም አሁንም መልስ ያላገኘንለት ነገር አለ። እኔ ከየት መጣሁ? እናትና አባቶቼ ለእኔ መፈጠር ምክንያቶች እንጂ ፈጣሪዎቼ አይደሉምና።
የእራሳችን አስገኝዎች እኛው እራሳችን ልንሆን ደግሞ በፍጹም አንችልም። ስለሆነም ማሰብ እንድንችል አድርጎ የፈጠረን ፍጹም እና “ገባሬ ኩሉ” የሆነ ፈጣሪ መኖሩን በዚሁ እንረዳለን ማለት ነው፤ ይለናል ዴካርት። የፍጽምና ባህሪ ያለው ፈጣሪ ደግሞ ጎደሎና ሐሰት የሆነ ነገር/ሐሳብ እንድናስብ አይፈቅድም፤ምክንያቱም ከባህሪው ጋር አይስማሙምና ማለት ነው። እዚህ ዓለም ላይ ያሉ ቁስ አካላትም (በሰው ውስጥ ያሉትንም ጨምሮ) እውነት ናቸው ማለት ነው። የተምታታ ሐሳብ እንዲኖረኝ የሚያደርገኝ ሙሉ የክፋት አቅሙን አሟጥጦ የሚጠቀም ያ “አወናባጅ ዲያብሎስ” ነው እንጂ ፈጣሪ ሊሆን አይችልም። የአወናባጁን ዲያብሎስ ምክር እየለየን ማሰብ ከቻልን፣ ወደ እርግጠኛ እውቀት የምናደርገው ጉዞ የተሳካ ይሆንልናል ማለት ነው።
ልዕለ መልካምነት ባህሪው የሆነ ፈጣሪ መኖሩን ማወቅ አለብን። እዚህ ዓለም ላይ ያለው እውነት ስለመሆኑ እርግጠኛ እንድንሆን የሚያደርገን ፈጣሪ ፍጹም እና የመልካሞች ሁሉ መልካም በመሆኑ፣ ለኛም ግልጽ የሆነና የጠራ ሐሳብን ይለግሰናል፡፡
ዳካርት፤ ግልጽነት፣ ልዩነት እና አለመፋለስን እንደ ሒሳብ ቀመር፣ የአንድን ጉዳይ እውነተኝነት/እርግጠኝነት የምንመዝንባቸው አድርጎ ስለቀመራቸው በቤተሰቡ ስያሜ “”የካርቴዚያን ዲበ አካል” ተብሎ ተሰይሞለታል።
የአውሮፓዊያን የፍልስፍና አስተምህሮ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦች መልስ ለመስጠት መፍጨርጨሩ አልቀረም፡፡ (ፈላስፋው አማኝ ነኝ አሊያም ኢ−አማኒ ነኝ ቢልም)። የቀደመው የአውሮፓ ፍልስፍና የሳይንስን እና የመጽሐፍ ቅዱስን ግጭት፤ የመጽሐፍ ቅዱስን ረቂቅነት ማስገንዘብ፤ ወይም ሳይንስ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያፈርሳት የሚከሰተውን ባዶነት መተንተን የሚመሳስሉ ሐሳቦች ያደሉበታል። የዴካርት አካሄድም ከዚሁ የተለየ አይመስልም። የስህተቶች ሁሉ ምንጭ አወናባጁ ዲያብሎስ ነው ይለናልና። “I will suppose therefore that ………rather some evil genius of the utmost power and cunning has employed all his energies in order to deceive me.”
በኛ አባቶች ትምህርት ዘንድ ደግሞ አንዳንድ ለየት ያሉ ታሪኮችን እንሰማለን። እኛው እራሳችን በራሳችን ፈቃድ የምናመነጫቸው የክፋት ሐሳቦች አሉን።
ከስሜት ህዋሶቻችን ከቅዠታችንም ባሻገር የሆኑ የክፋት ሐሳቦች። በአንድ ገዳም ውስጥ የተከሰተ እንደሆነ የሚነገር አንድ ታሪክ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን ይመስለኛል። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ የአንድ ገዳም ኃላፊ/አበመኔት/ ገዳማዊያኑን እየጎበኙ ሳለ ወደ አንድ አባት ዋሻ ይዘልቃሉ። እናም አባትን እንቁላል በጧፍ ሲጠብሱ ያገኟቸዋል፤ የጾም ወቅት ነበርና በመጥበሻ ቢጠብሱት እንቁላሉ ሊሸትና ሊታወቅባቸው ስለሆነ በጧፍ ተያይዘውታል። ኃላፊውም ይደነግጡና “ኧረ! ኧረ! አባቴ ምን ነካዎት? በጾሙ እንቁላል?” ይላሉ። ባለዋሻውም ተጸጽተው “ኧረ ይቅር ይበሉኝ ሰይጣን አሳስቶኝ ነው” ማለት። ጋሽ ዲያብሎስ ደግሞ ወዲያው ከተፍ አለና “ኧረ ይቺን እንቁላል አጠባበስ ያለዛሬም አላየኋትም” አለ አሉ።
የኛ አባቶች እንዲህ ናቸው፤ ደረቅ እና ረቂቅ ሐሳቦችን በምሳሌና በተረት እያዋዙ ማቅረቡን ተክነውበታል። እንዲች ያለች መጽሐፍ ቅዱሳዊ አንድምታና ፍልስፍና ለኢትዮጵያዊ ካልሆነ ለአውሮፓዊ የምትቻለው አይመስለኝም።

Published in ጥበብ

ሲደክማችሁ በጣም እንወዳለን 
“በጣፋጩ ደማችሁ” መዓዛ የምንሳብ ሊመስላችሁ ይችላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ከደማችሁ ይልቅ እኛን ወደ እናንተ እንድንሳብ የሚያደርገው፣ የምትተነፍሱት የተቃጠለ አየር (ካርቦንዳይኦክሳይድ) ነው፡፡ በጣም ስትተነፍሱ ብዙ ካርቦንዳይኦክሳይድ (Co2) ታስወጣላችሁ፡፡ ስለዚህ በተለይ ብዙ ሠርታችሁ ወይም የሰውነት እንቅስቃሴ አድርጋችሁ ሲደክማችሁ በጣም ታስጐመዡናላችሁ፡፡
የቢራ ፍቅር
አንዳንዶቻችን ቢራ እንወዳለን፡፡ የሚገርም ይመስላል አይደል? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ የእኛ ፍቅር ከቢራው (ከመጠጡ) አይደለም። እናንተን ስለሚጠቁመን ነው የምንወደው፡፡ እንዴት መሰላችሁ? ቢራ ስትጠጡ የቆዳችሁ ንጥረ ቅመም (ኬሚስትሪ) ይለወጣል፡፡ ያ ነገር ወደ እናንተ ይስበናል፡፡ ለዚህ ነው ቢራ መጠጣታችሁን የምንወደው፡፡

ነፍሰጡር ነሽ? በጣም ታስፈልጊናለሽ
እርጉዝ ሆነሽ መውለጃሽ ሲቃረብ ይደክምሻል። ስለዚህ፣ ብዙ ጊዜ እየተነፈስሽ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ወይም የተቃጠለ አየር ታስወጫለሽ። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ መውለጃሽ ሲደርስ፣ ሆድሽ ከፍተኛ ሙቀት ይፈጥራል።
አንዳንዶቻችንን ይህ ሙቀት ወደ አንቺ እንድንሳብና እንድንከብሽ ያደርገናል። እንግዲህ ማሙሽና ሚሚ እናዝናለን! የእኛም ሕይወት አይደል? ምንም ማድረግ አንችልም፡፡
በወባ ትንኝ መነደፍ አትወዱም አይደል? ሴቷን ትንሽ ወቀሱ
ነገር ግን እኛ ሴት የወባ ትንኞች ይህንን ወቀሳ ስለማንሰማ ተውት፡፡ በእርግጥ አንድ የማይካድ ሐቅ አለ፡፡
ወንድ ወባ ትንኞች፣ የሰው ደም በፍፁም ስለማይመገቡ፣ ስማቸውን በከንቱ አታጥፉ፤ መወቀስ ካለብንም እኛ ሴቶቹ ነን። ወንዶቹ የሚያስፈልጋቸውን የተመጣጠነ ምግብ (ኑትሪሽን) በሙሉ የሚያገኙት ተክሎች በአበባቸው ውስጥ ከሚያዘጋጁት ጣፋጭ ፈሳሽ (Nectar) ነው፡፡ እኛ ሴቶቹ ግን የሰው ደም ዕንቁላላችንን የሚያሳድግ ፕሮቲን ስላለው እንፈልገዋለን፡፡ የሰው ደም ከተመገብን በኋላ፣ ከ100 እስከ 400 ዕንቁላሎች መጣል እንችላለን፡፡
የሚሸት እግር እንወዳለን
እኛ ሴቶች ከሰውነታችሁ ክፍል የምንጠላው የለም፡፡ በእርግጥ ስንቶቻችሁ፣ እግሮቻችሁን ከLimburger cheese 10 እጅ የበለጠ እንደምንወድ አሳይተዋል። ነገር ግን ዛሬ እውነቱን አይደል የምንነጋገረው? ውሸት ምን ያደርጋል? እኛ በፍቅር የምንወደው የሰውነታችሁ ክፍል እጃችሁን ነው፡፡
የዳንስ ቦታ፤ ሠርግና ምላሻችን ነው
ፓርቲ (ዳንስ) ቤት በዛ ያሉ ሰዎች እየጠጡ ሲጨፍሩ፣ በጣም በርከት ያለ የተቃጠለ አየር (ካርቦንዳይኦክሳይድ) ያስወጣሉ ወይም ይተነፍሳሉ። ያ ሲሸተን ወደዚያ እንበራለን፡፡ እዚያ ከደረሰን በኋላ መኻል ላይ እጅብ ብለው ከሚደንሱት ይልቅ ከቡድኑ ውስጥ ነጠል ያሉትን ማጥቃት ይቀለናል፡፡
ገላጣ ቦታ አንወድም
ለመኖሪያነት፣ በጣም ጥቅጥቅ ያለና በጣም ያደጉ ተክሎች ያለበትን ስፍራ እንመርጣለን። ጨለም ያለና ብዙ እርጥበት ካለው ደግሞ በጣም ይመረጣል። የመዋኛ ገንዳው ውሃ ካልቋጠረ፣ የአካባቢው ቁጥቋጦ ከተመለመለ፣ ሳሩ አጥሮ ከታጨደ ያንን ግቢ ለመኖርያነት ብዙም አንመርጠውም፡፡ የረጋ ውሃ ወይም ኩሬ እንዲፈስ ወይም እንዲጠፋ ከተደረገ፣ መሰደዳችን ነው፡፡ ምክንያቱም ያ ስፍራ’ኮ የዕንቁላላችን መጣያ ነበር!
ፀረ-ነፍሳት ያልሆነ ተክል ሲተከል ጮቤ እንረግጣለን
Deet እና Picardin የተባሉ ክፍሎች ፀራችን ናቸው። ፀረ-ነፍሳት መርዝ ስላላቸው እነሱ ሲተከሉ፣ ድራሻችን ነው የሚጠፋው፡፡ የማንወዳቸው ሌሎች ተክሎችም አሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ግን፣ የተለያዩ የደም መምጠጫ አካላችንን ይዘጋሉ፡፡ ሎሚና ባህር ዛፍ ያላቸው መርዝ ደከም ያለ ቢሆንም አንወዳቸውም፡፡
Co2 የሚያመነጭ መሳሪያ፤ ለእኛ ደስታችን ነው
ካርቦንዳይኦክሳይድ (Co2) ስለምንወድ እኛን አሳስታችሁ ለማጥመድ ካርቦንዳይኦክሳይድ የሚያመነጭ መሳሪያ ግቢያችሁ በመትከላችሁ፣ “ብልጥ ነን” ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ብልጥ አይደላችሁም፡፡ ምክንያቱም መሳሪያው፣ እኛን ወደ ወጥመዱ ከመክተት ይልቅ፣ በግቢያችሁ፣ የወባ ትንኞችን ቁጥር ሊያበዛው ይችላል። UV (አልትራ ቫዮሌት) በተባለ ጨረር፣ እኛን ለማጥፋት የተሞከረው ዘዴም፣ እርባናው ይህን ያህል አይደለም። ምክንያቱም የማጥመጃው ዘዴ ከሚገድላቸው ነፍሳት መካከል፣ የወባ ትንኞች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
የዌስት ናይል ቫይረስ (West Nile) ጉዳት የከፋ ነው-
ይህ ቫይረስ በምዕራብ ናይል አካባቢ የሚገኝ ነው። የሚያደርሰውን ጉዳት አስከፊነት ለመረዳት በጣም ቀላል ነው፡፡ በመጀመሪያ ቫይረሱ ያለባቸውን ወፎች እንነክሳለን፡፡ ከዚያም ሰዎችን በመንደፍ ቫይረሱን እናሰራጫለን፡፡ የበጋ ወራት ማብቂያ ደግሞ በቫይረሱ የተጠቁ ወፎችን ለመንደፍ ጥሩ ዕድል ይፈጥርልናል፡፡
ሁነኛ ነጥቦች
የወባ ትንኝ በምትመገብበት ጊዜ የምትመጠው ከአንድ ጠብታ ደም ያነሰ ነው፡፡ በሰውነታችን 5 ሊትር ደም ይገኛል፡፡
የወባ ትንኝ በሰዓት ከአንድ እስከ አንድ ተኩል ኪ.ሜ ትጓዛለች፡፡
በመላው ዓለም ከ3ሺ በላይ የወባ ትንኝ ዝርያ አለ፡፡ 176ቱ የሚገኙት በአሜሪካ ነው፡፡
ጨዋማ በሆነ ረግረግ ስፍራ የሚኖሩ የወባ ትንኞች ምግብ ፍለጋ ከ64 ኪ.ሜ በላይ ሊሰደዱ ይችላሉ፡፡
የሰው ልጅ ዝርያ ጂኖች (genes) ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደሚሸጋገሩ የሚያጠናው ሳይንስ (genetics) ከመቶ ሰዎች 85ቱ፣ ለወባ ትንኝ ንድፊያ የተጋለጡ ናቸው ይላል፡፡
ምንጭ፡- (Reader’s Digest USA July, 2013)

Published in ዋናው ጤና

የጋምቢያው ፕሬዚዳንት ያያ ጃሜ “ኤች አይቪን አድናለሁ” በማለታቸው
ለረጅም ጊዜ ከሚዲያ ዘገባ የማይጠፉ ፕሬዚደንት አድርጓቸው ነበር፡፡
በቅርቡ ደግሞ አገራቸው ከኮመንዌልዝ አባልነቷ መውጣቷን በድንገት ማወጃቸውን ተከትሎ የዓለም መነጋገሪያ ሆነዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ ከ“ኒው አፍሪካን” መፅሄት ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ለጋዜጣው በሚመች መልኩ ተጠናቅሮ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ጋምቢያ ከኮመን ዌልዝ አባልነቷ መውጣቷ የመነጋገሪያ ርአስ ሆኗል፡፡ ከአርባ አምስት አመት በኋላ ከአባልነት ለመውጣት ለምን ወሰኑ?
ዜናው አነጋገሪ ሊሆን አይገባም ነበር፡፡ ጋምቢያ ይህን ውሳኔ የወሰነችው ከቅኝ ግዛት ጋር ከተያያዙ ነገሮች ነፃ መሆን ስለምትፈልግ ነው፡፡ በተለይም ምንም አዲስ ነገር በሌለበት ሁኔታ ውሳኔ የሚሰጠው ከአንድ ወገን ብቻ ሲሆን አባል መሆን ለምን ይጠቅማል፡፡ እኛን ሳያዳምጥ “ይህን አድርጉ” እያለ በሚያዝና ብቻውን በሚወስን ተቋም አባል ከመሆን መውጣቱ የተሻለ ነው፡፡ ስለዚህ ነፃነታችንን ካገኘን ከአርባ ስምንት አመት በኋላ ቅኝ ግዛት እና እንግሊዝ በቃን ብለናል፡፡ ወደኋላ መለሱን እንጂ የትም አላደረሱንም፡፡ የዚህ አመት ዋናው መፈክራችን “እንደ ባህላችንና እንደ ሀይማኖታችን እንኑር” የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ኮመን ዌልዝ ሀይማኖታችንም ባህላችንም አይደለም፡፡ ከቅኝ ግዛት ጋር ንኪኪ ባላቸው ተቋሟት አባል መሆን አንፈልግም፡፡ በጋምቢያውያንነታችን መቀጠል እንፈልጋለን፡፡
በመንግስታቱ ድርጅት ያደረጉት ንግግር በመገናኛ ብዙኀን በአሉታዊ መንገድ መዘገቡን ተከትሎ አባልነትዎን መሰረዝዎስ?
በጣም የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ ከአንድ ሰውጋር ያለሽን ግንኙነት ለማቋረጥ በመጀመሪያ ከዛ ሰው ጋር ችግር መፈጠር አለበት የሚል አስተሳሰብ አለ። ይህ ለኔ ትክክል አይደለም፡፡ ችግር ካለ ችግሩን መፍታት ነው፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ኮመን ዌልዝ የቅኝ ግዛት ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ ከአሁን በኋላ አባል አይደለንም፡፡ በነገራችን ላይ ከኮመን ዌልዝ ብቻ ሳይሆን ከቅኝ ግዛት ጋር ግንኙነት ካለውና የቅኝ ግዛት ዘመንን ከሚያስቀጥል ማንኛውም ተቋም ጋር ግንኙነት አይኖረንም፡፡ ምክንያቱም ከቅኝ ግዛት ያተረፍነው ድህነት፤ ኋላቀርነት፤ብዝበዛ እና ባርነትን ነው፡፡
በዚህ ዘመን ለባርነት ተጠያቂ ከሆኑ አገሮች ጋር ትስስር ሊኖረን አይገባም፡፡ አይሁዳውያን እና ሌሎች ህዝቦች ለደረሰባቸው በደል ካሳ ተከፍሏቸዋል፡፡ አፍሪካን ግን ማንም ዞር ብሎ አላያትም፡፡ ባርነትንና ቅኝ ግዛትን ያመጣችብን እንግሊዝ ካሳ ልትከፍለን ቀርቶ ይቅርታም አልጠየቀችንም፡፡ ጋምቢያውያን በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር በነበሩባቸው አመታት ማንም ሳይንቲስቶች እና ዶክተሮች እንዲሆኑ ስልጠና አልተሰጣቸውም፡፡ ለሌሎችም አፍሪካውያን እድል አልተሰጠም፡፡ እኛ ልክ እንደ ሌላው የሰው ዘር አይደለንም?
ምእራባውያኑ አሁንም አፍሪካ ኋላ እንድትቀር ይፈልጋሉ ብለው ለምን ያምናሉ?
አንቺ አለምን እየዞርሽ የምታይ ጋዜጠኛ ነሽ፡፡ ልክ እንደ ዱባይ ወይም የመካከለኛው ምስራቅ አገራት በቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ያደጉ የአፍሪካ አገሮችን ልትነግሪኝ ትችያለሽ? ሌሎችን የምትከተይ ከሆነ መምራት አትችይም፡፡ እኛ አፍሪካውያን ለዘመናት ስንከተላቸው ኖረናል፡፡ አሁንም እየተከተልናቸው ነው፡፡ በቃ ካላልን ወደፊትም እንከተላቸዋለን፡፡ ኋላ የቀረነውም ለዚህ ነው፡፡ ለአፍሪካ ያለኝ መልእክት መከተሉን አቁመን መሪ እንሁን ነው፡፡ በአፍሪካ እና በምእራባውያኑ ግንኙነት አፍሪካ ተጠቃሚ እየሆነች አይደለም፡፡ ተጎጂ ናት፡፡ እኔ እና ጋምቢያ ማንንም መከተሉን ትተን የራሳችንን ሀይማኖት፣ ባህል እና እምነቶች መከተል ጀምረናል፡፡ አፍሪካ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለች አህጉር ሆና ለምን ድሀ ሆነች? አውሮፓውያኑ ምን ስለሆኑ ነው አፍሪካውያን ምን መስራት እንዳለባቸው የሚያስተምሩት? ከቅኝ ግዛት አንስቶ እስካሁን ራሳቸውን የአፍሪካ ፈጣሪ አድርገው ያስባሉ፡፡ ጋምቢያ በቃ እያለች ነው፡፡ በሙዚቃቸው መደነስ ስታቆሚ አምባገነን ይሉሻል፡፡
ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የእርስዎን ውሳኔ የሚከተሉ ይመስልዎታል?
የሚጠቅመንን መከተል ጥሩ ውሳኔ ነው፡፡ ወደ ኋላ የሚመልስሽን የምትከተይ ከሆነ፣ አላዋቂ ብቻ ሳይሆን የምትሆኚው በህዝብሽ ፍላጎት እየሰራሽ አይደለም ማለት ነው፡፡ ቅኝ አገዛዝና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በማንኛውም መልኩ ከአፍሪካ መወገድ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ትርፉ ውርደት እና ስድብ ነው፡፡
የሌሎች ድርጅቶች አባልነትዎን ግን አልተዉም?
ውሳኔዬ ወደ ሌላ መተርጎም የለበትም፡፡ እኔ ያልኩት በጣም ግልፅ ነው፡፡ ከቅኝ ግዛት እና ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ጋር ከተያያዘ ማንኛውም ተቋም ጋር ግንኙነት አንፈልግም፡፡ ይህ ማለት ግን ሌሎች የአለም አቀፍ ተቋማትን ያጠቃልላል ማለት አይደለም፡፡ ኮመንዌልዝ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ተቋም ብቻ ሳይሆን የምርጫ ሂደትም የለውም፡፡ አንድ ግለሰብ የህይወት ዘመን መሪ ነው፡፡ ይሄ ምን አይነት ዲሞክራሲ ነው? ተረዳሽኝ?
እንግሊዞቹ በነሱ ላይ ብቻ የዘመቱ አይመስላቸውም?
እንግሊዞቹ ኮመንዌልዝ የነሱ እንደሆነ ካሰቡ ለመውጣታችን ጥሩ ምክንያት ይሆናል፡፡ ለምንድነው የራሳቸው እንደሆነ የሚያስቡት?
ሌላው ተመሳሳይ ድርጅት ደግሞ አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱን ከሚመሩት መካከል በእርስዎ መንግስት ያገለገሉት ፋቱ ቤንሶዳ ይገኙበታል፡፡ ድርጅቱ ከአፍሪካ መሪዎች ተቃውሞ እየገጠመው ነው፡፡ በፍርድ ቤቱ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ፍርድ ቤቱ የቅኝ ገዢ ተቋም አይደለም፡፡ በቅርቡ ነው የተቋቋመው፡፡ ነገር ግን በሌሎቹ ተቋሟት ላይ እንደምናደርገው አባል ለመሆን እጅግ በጣም ፈጣኖች ነን፡፡ አባል እንሆንና ካፀደቅነው በኋላ ምን እንደሚል ማንበብ እንጀምራለን፡፡
ከዛ ነገሮችን ወደ ኋላ ለመመለስ አስቸጋሪ ይሆንብናል፡፡ ዘለን ከአንዱ ወደ አንዱ አንሳፈር ብዬ ጓደኞቼን አስጠንቅቄያለሁ፡፡ ሁሉም አውቶብስ ውስጥ መዳረሻውን ሳናውቅ እንሳፈራለን። ሾፌሩ በመሀል ላይ “አፍሪካውያን ውረዱ” ሲል ለምን ተሳፈርን ብለን መጠየቅ እንጀምራለን። ከአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባላት መካከል አፍሪካ ብዙውን ድርሻ ትይዛለች፡፡ ፍርድ ቤቱ በእግሩ እንዲቆም ያደረገችው አፍሪካ ናት፡፡ እኔ መጀመሪያም ተናግሬ ነበር፣ዝም ብለን ከመቀላቀላችን በፊት ምን እንደሚል በጥሞና እንየው፡፡ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በራሳችን ፈቃድ ተጎጂ የምንሆንበትን ጉዳይ ቀድመን ተስማምተናል። የፕሬዚደንት አልበሽርን ክስ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ሲቃወሙት፣ አንዳንዶች ደግፈውታል፡፡ ፍርድ ቤቱ የአፍሪካ ህብረትንም ሳያሳውቅ መሪዎችን እንዲከስ ይስማማሉ፡፡ ድርጅቱ የአውሮፓ አገራት መሪዎችን ያለ አውሮፓ ህብረት ፈቃድ መክሰስ ይፈቀድለታል? ይህ ትልቅ ስድብ ነው፡፡ አንድ ክስ የሚቀርበው ወይ በክስ አቅራቢ አገር ወይም በፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ነው፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ፍርድ ቤቱ ላይ ሲጮሁ አፍራለሁ፣ምክንያቱም ከአልበሽር ጉዳይ በስተቀር የሌሎቹ ክስ የቀረበው በራሳቸው በአፍሪካ መንግስታት ነው፡፡ ራሳችን ክስ እናቀርብና መልሰን አይሲሲ ዘረኛ ነው እንላለን፡፡
ስለዚህ አይሲሲ አፍሪካውያንን ያድናል በሚለው አይስማሙም?
አዎ አልስማማም፡፡ አፍሪካ ችግር ካለባት ችግሯን በራሷ መፍታት አለባት፡፡ ችግሩን ወደ አፍሪካ ህብረት ከማምጣት ይልቅ ወደ አይሲሲ መውሰድ አያሳፍርም?
ጋምቢያዊቷ ሚስ ቤንሶውዳ በፍርድ ቤቱ እያከናወኑት ባለው ተግባር ይኮራሉ ማለት ነው?
እሷ አለም አቀፍ ሰራተኛ ናት፡፡ ኩራት የሚሰማኝ ጋምቢያዊት ስለሆነች ሳይሆን የአፍሪካ ሴት ስለሆነች ነው፡፡ ይህ ቦታ ቀደም ሲል በአፍሪካውያን የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ዛሬ በአፍሪካዊት ተይዟል፡፡ ስለዚህ ከተቋሙ ጋር መተባበር አለብን፡፡ ለአይሲሲ ስል ሳይሆን ለእውነት ስል፡፡
ስምዎ ብዙ ጊዜ በጥሩ አይነሳም፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም ስልጣን ከያዙ በኋላ ምን ሰራሁ ይላሉ?
ከጥቂት አመታት በፊት ምንም ዩኒቨርሲቲ አልነበረም፡፡ ኮመንዌልዝን የተውንበት አንዱ ምክንያት ይሄ ነው፡፡ እንግሊዞቹ አራት መቶ አመታት ሲገዙን፣ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብቻ ነው የሰሩት፡፡
እውነትዎትን ነው?
እየነገርኩሽ፡፡ ነፃ ከወጣን በኋላ ለ30 ዓመታት ያስተዳደረው መንግስት ይባስ ብሎ አንድም ት/ቤት ወይም ሆስፒታል አሊያም ዩኒቨርስቲ አልገነባም፡፡ የብሪቲሽ ቅኝ አገዛዝ ቢያንስ አንድ ት/ቤት ሰርቷል - ለጥቂቶች ቢሆንም፡፡ እንግዲህ ብሪቲሾች በአራት መቶ አመት ውስጥ አንድ ትምህርት ቤት ከሰሩ ኮሌጅ ወይም ዩኒቨርሲቲ ለመስራት ስንት ተጨማሪ አመታት የሚፈልጉ ይመስልሻል? ወደ አንድ ቢሊዮን አመት፡፡ ከኮመንዌልዝ ለመውጣት ስለመወሰናችን ማንንም እንዳላማከርን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ እነሱ የሚፈልጉት በቅድሚያ ነግረናቸው ፈቃዳቸውን እንድናገኝ ነው፡፡ እኛ የማንም አገልጋይ አይደለንም። እኛ በየአመቱ ከኮመንዌልዝ ከምናገኘው ጥቅም ይልቅ የምንከፍለው ይበልጣል፡፡
በምእራብውያኑ መገናኛ ብዙሀን እና በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ዘንድ አምባገነን ተብለው ነው የሚታወቁት፡፡ የግብረሰዶማውያን መብትን ጨምሮ በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ጥሰት ይወቀሳሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አዎ የልማት አምባገነን ነኝ፡፡ የለውጥ አምባገነን ነኝ፡፡ በሌሎች ትእዛዝ የማይሰራ አምባገነንም ነኝ፡፡ ጋምቢያ ውስጥ ግን የህዝብ አገልጋይ ነኝ፡፡ ረጅም መንገድ መጥተናል፡፡ ገና ረጅም መንገድ ይቀረናል። የምንመካው በፈጣሪ እና እንደ ሰው በሚቆጥሩን አገሮች ነው፡፡ ግብረሰዶማዊነትን ጋምቢያ ውስጥ በፍፁም አንፈቅድም፡፡ የመንግስት አስተዳደርን በተመለከተ ደግሞ እነሱ አፍሪካን ይገዙ በነበረ ጊዜ አፍሪካውያን በምርጫ ተሳትፈው ያውቃሉ? ሰብአዊ መብት፣ ነፃነትና መልካም አስተዳደር ቅኝ ገዢዎችን የሚመለከት አይመስልም እኮ፡፡
ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን በመግደልም ይወነጀላሉ---
ሰውን ሰቅሎ መግደል አፍሪካ ውስጥ የመጣው በቅኝ ገዢዎች ነው፡፡ ከቅኝ ግዛት በፊት አፍሪካ ውስጥ የነበረው ክፍያ ነው፡፡ ሰው የሚሞተው በጦርነት ላይ ብቻ ነበር፡፡ የጭካኔ አይነት አፍሪካውያን ላይ ሲፈፅሙ ኖረው የሰብአዊ መብት አስተማሪ መሆን ይፈልጋሉ፡፡ አፍሪካውያንን በአንድ መርከብ ላይ እንደ ሰርዲን አሽጎ ወስዶ፣ አሜሪካን ገበያ ላይ በጨረታ ከመሸጥ፣ ከዛም ከውሻ ያነሰ ኑሮ እንዲኖሩ ከማድረግና አህጉሪቱን ከመዝረፍ በላይ ምን የመብት ጥሰት አለ? ለዚህ ኢ-ሰብአዊ ድርጊታቸው ይቅርታ እንኳን ያልጠየቁ፣ አፍሪካን ስለ ዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት ሊያስተምሩ ይችላሉ?
ጋምቢያ የነዳጅ ሀብት አላት?
አዎ አለን ፡፡ ጥቅም ላይ ያላዋልናቸው ማእድኖች እና ነዳጅ አለን፡፡ እስከ ዛሬ ነዳጃችንን ያላወጣነውም አምስት በመቶ ብቻ ለእኛ ተሰጥቶ የቀረው ሌሎችን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስምምነት መገዛት ስለማልፈልግ ነው፡፡
የተፈጥሮ ሀብትን ለልማት ማዋልንን እና ግሎባላይዜሽንን እንዴት ያዩታል?
ግሎባላይዜሽን ማለት የተፈጥሮ ሀብትን ዝም ብሎ መስጠት አይደለም፡፡ ሁሉም ኩባንያዎች መጥፎ ናቸውም አላልኩም፡፡ ምርጫ ሊሰጠን ይገባል፡፡ ሞራል ካላቸው ሀብቱ የአፍሪካውያን እንደሆነ ከሚያምኑ ጋር እንሰራለን፡፡ ቻይና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለአፍሪካ አምባገነኖች እርዳታ ታደርጋለች የሚል ተደጋጋሚ ስሞታ እንሰማለን፡፡ ግን እነሱ ራሳቸው የቻይናን ካፒታል ኢንቨስትመንት ይቀበላሉ፡፡ የቻይና የአፍሪካ አጋር ሆኖ መምጣት ለአፍሪካ ምርጫ ሰጥቷል፡፡ የቻይናን ስም የሚያጠፉትም ለዚህ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ብሪክስ አገሮች እየመጡ ነው፡፡ ዋናው ነገር ከሚጠቅመን ጋር መስራት ነው፡፡ ሁሉም ምእራባውያን ደም መጣጮች አይደሉም፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ይቺ ከተማ ‘ዘመናዊነት’ አፍኖ ትንፋሽ ሊያሳጥራት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… በፊት ጊዜ “ድንቄም!” የምትል ቃል ነበረች፡፡ እሷ ቃል ‘አቧራዋ ተራግፎ’ እንደገና ጥቅም ላይ ትዋልንማ፡፡ ልክ ነዋ… “ድንቄም!” የምንልባቸው ነገሮች በዙብና! እናማ…የዚች ‘የአፍሪካ መዲና’ ከተማችን የ‘ዘመናዊነት’ ማሳያዎች ድንቄም እያስባሉን ነው፡፡
በቀደም እዚህ የፈረደበት ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በረፋዱ ሰዓት ቢበዛ አሥራ ሦስትና አሥራ አራት የማይበልጡ ሚጢጢ እሷና እሱ ‘ኪሲንጉን’ ያጦፉት ነበር፡፡ (ስሙኝማ… እዛ ሰፈር እኮ… አለ አይደል… የማይታይ ጉድ የለም፡፡ “ጉድ!” የምንለው የእኔ ቢጤዎቹ እንደሆንን ልብ ይባልንማ!)
ልጅቱ ለጓደኛዋ ምን ትላታለች? “አንድ የማላውቀው ሰውዬ ዛሬ ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ?”
“ምን አለሽ?”
“ፍቀጂልኝና ልሳምሽ አለኝ”
“እና በጥፊ አጮልሽው?”
“አዎ፣ ስሞኝ ሲያበቃ አጮልኩት”
ዘንድሮ እኛ ግን…አይደለም ከተሳሙ በኋላ ማጮል… እንደውም “አትሳመኝና አጠናግርሀለሁ…” ብለው ‘እጅ የሚጠመዝዙ’ እንዳይመጡ ፍሩልኝማ!
ከ‘ኪሶሎጂ’ ሳንወጣ ይቺን ስሙኝማ…እሱዬው እሷን ምን ይላታል… “ጫፍሽን ሳልነካሽ መአት ጊዜ ደጋግሜ ልስምሽ እችላለሁ፡፡ ካልቻልኩ አምስት ብር እቀጣለሁ፡፡” እሷዬው የእልህ ሆነና “እሺ…” ትላለች፡፡ እሱዬው ደጋግሞ ይመጨምጫታል፡፡ “ሳልነካሽ አይደል እንዴ ያልከው! ይኸው ነካኸኝ አይደል!” ስትለው ምን ቢላት ጥሩ ነው… “በቃ፣ አምስት ብርሽ ይኸውልሽ!”
እናላችሁ… ስልጣኔና ‘ጥጋብ’ እየተደበላለቁ የምንይዘው እያሳጣን ነው፡፡ አባቶቻችን “ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ…” የሚሉት የእውነትም ወደው አልነበረም፡፡
ታዲያማ… ወንበር ላይ ስንወጣ የምንጠግብ፣ የባንክ ደብተራችን ወደ ‘ሲክስ ዲጂት’ ሲያድግ ‘ጥጋብ ሻኛ የሚጨምርልን’፣ መኪና ቢጤ ስንይዝ ‘ጥጋብ ሻኛ የሚጨምርልን’፣ ‘የዘመኑ ሰው’ ወዳጅ ስናደርግ ‘ጥጋብ ሻኛ የሚጨምርልን’፣ ምን አለፋችሁ… በትንሹም በትልቁም ነገር ‘ጥጋብ ዝሆን የሚያሳክለን በዝተናል፡፡
አንድ መጽሐፍ በስማችን ስናወጣ ‘ጥጋብ ሻኛ የሚጨምርልን’፣ በመድረክ ግጥም አዳራሹ ስላጨበጨበልን ‘ጥጋብ ሻኛ የሚጨምርልን’፣ በፊልም ወይም በደራማ “አሪፍ! አሪፍ!” ስንባል ‘ጥጋብ ሻኛ የሚጨምርልን’፣ በኳስ ላይ “እንደ ሩኒ… እንደ ሜሲ ምናምን ስንባል ‘ጥጋብ ሻኛ የሚጨምርልን’፣ …ብቻ፣ ከምንጠግብባቸው የማንጠግብባቸውን ምክንያቶች መዘርዘሩ ይቀላል፡፡
እናላችሁ…ችግሩ ምን መሰላችሁ…ብዙ ጊዜ ‘ዘመናዊነት’ ጋር የሚያያዙት ነገሮች መነሻቸው ጥጋብ ነው፡፡ ሻኛን የጨመረ መስሎ አእምሮን ተከራይ ያጣ ቤት የሚያስመስል ጥጋብ፡፡
እናላችሁ… አናት ላይ የወጣ ‘ጥጋብ’ ከዘመናዊነት እየተቆጠረ “በአማርኛ ዛሬ ቀኑ ስንት ነው?” የምንል እየፈላንላችሁ ነው… ‘ላይኛው ቤት’ አእምሮ ሲታደል ‘ቀሪ’ የነበርን፡፡ ‘ጨ’ እና ‘ቀ’ የተባሉ ፊደላትን ‘ቸ’ እና ‘ከ’ ካላልን ኋላ ቀርነት የሚመስለን ጥጋባችን ዘመናዊነት የሚመስለን እየፈላን ነው፡፡
የቋንቋ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አንድ የኬጂቢ ሰላይ በመናፈሻ ውስጥ ሲንጎራደድ አንድ ሸምገል ያለ ሰው መጽሐፍ ሲያነብ ያገኛል፡፡ እናላችሁ… “ምን እያነበብክ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየውም “እብራይስጥ ቋንቋ እያጠናሁ ነው…” ይለዋል፡፡
ሰላዩም “እብራይስጥ ማጥናት ምን ያደርግልሀል? እሥራኤል መግቢያ ቪዛ ለማግኘት ዓመታት ይፈጃል፡፡ እስከዛ ደግሞ ልትሞት ትችላላሀ፡፡” ሲል ሞራሉ ላይ ይረማመድበታል፡፡
ሰውየውም “እብራይስጥ የማጠናው ሞቼ መንግሥተ ሰማያት ስሄድ አብረሃምና ሙሴን እንዳናግርበት ነው፡፡ እብራይስጥ መንግሥተ ሰማያት ወስጥ የሚናገሩት ቋንቋ ነው” ይላል፡፡
የኬጂቢው ሰላይም “ስትሞት መንግሥተ ሰማያት ሳይሆን ገሀናም ብትገባስ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “እዛማ ቋንቋው ሩስያኛ ስለሆነ አይቸግረኝም።”
ሀሳብ አለን… እኛ የምንሄድበት ገሀነም (መቼም ከሁሉም ጋር አይቀላቅሉንም!) አፍ መፍቻ ቋንቋው ምን እንደሆነ ይጠናልንማ!
እናላችሁ… ከዚህ በፊት ያወራናት የአሥራ አራት ዓመት ልጇ ሲጋራ ስታጨስ መያዟ ሊነገራት የተጠራች እናት… “እኔ አስተምሩልኝ አልኩ እንጂ ሲጋራ ማጨሷን ተቆጣጠሩልኝ አልኩ!” አይነት ‘ወላጆች’ እየበዙ ሲሄዱ የምር ያሳስባል፡፡ ይቺ እናት ጥጋቧ አናት ላይ ስለወጣ …የአሥራ አራት ዓመት ልጇ ሲጋራ ማጨስ የ‘ዘመናዊነት’… የመሰልጠን ‘ግሪን ካርድ’ ይመስላታል፡፡ ይቺኛዋ መጀመሪያ ላይ አእምሮ ሲታደል ላልነበሩ የተዘጋጀ ‘ማራዘሚያ’ ላይም ያልተገኘች መሆን አለባት፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
በሌላ ቦታ ሚጢጢ ልጇ በጣም አጭር ሚኒስከርት ለብሳ ትምህርት ቤት መምጣቷ ሊነገራት የመጣች እናት፣ ከልጇ የባሰ አጭር ለብሳ ብትመጣ ጊዜ፣የትምህርት ቤቱ ሰዎቹ ሀሳባቸውን ለውጠው ትተውታል፡፡ ለሴትየዋ ገና ሚጢጢ ልጇ ሚኒስከርት መልበሷ የዘመናዊነት ምልክት ነው፡፡
ስሙኝማ…አንድ ጊዜ እንዳወራነው…አለ አይደል… “ልጄ የአሜሪካ ፓስፖርት አገኘ…” “ልጄ የእንግሊዝ ዜግነት አገኘች…” እየተባለ ቅልጥ ያለ ድግስ የሚደገስበት አገር ሆነናል እኮ! ኮሚክ እኮ ነው… ማነነትን አውልቀው ሲጥሉ “ይትባረክ እንደ አብረሀም…” አይነት ውዳሴ… እየሄድን ያለንበት ‘አቅጣጫ መጠቆሚያ የሌለው’ መንገድ ምን ያህል እንዳደነጋገረን የሚያሳይ አይመስላችሁም? (ጥያቄ አለን…ቦሶቻችን መሀል ሌላ ‘የክፉ ቀን ፓስፖርት’ ያላቸው አሉ የሚባለው እውነት ነው እንዴ! አሀ…አንዳንዴ የሚናገሩት ነገር ይሄ ሰውዬ ሌላ አገር አለው እንዴ እያስባለን ነዋ!”)
እናላችሁ… “አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው...” ብለን በአደባባይ፣ በተከበረው በትምህርት አደባባይ ስንለጥፍ፣ ህሊናችንን ትንሽ እንኳን የማይቆጠቁጠን…አለ አይደል… እንግሊዝኛ መናገር ‘ዘመናዊነት’ የሚመስለን ሰዎች የፈላንበት ዘመን ነው፡፡
(ስሙኝማ…እግረ መንገዴን በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየጻፍንም፣ እያነበብንም፣ እየተነጋገርንም መግባባት መሞከር ክፋት የለውም፡፡ እንደውም ከቋንቋው ዓለም አቀፍ ይዘት ልናገኝ የምንችለውን መረጃና፣ እውቀት እንደሚያሰፋልን የታወቀ ነው፡፡ ችግሩ የሚመጣው ግን እንግሊዝኛ የምንጠቀመው፣ ‘አማርኛ ቀሺም’ ስለሆነ አይነት የቀሸመ አስተሳሰብ ሲኖር ነው፡፡ እናማ…ሰዎች የቋንቋ ችሎታቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ አሪፍ ነው፡፡ ግን በእንግሊዝኛ ማሰብና በአማርኛ ወይንም በሌላ አገርኛ ቋንቋ ማሰብ ልዩነቱ የሀሳብ ክብደትና ቅለት ሳይሆን የተጠቀምንበት ቋንቋ ነው…አለቀ፡፡)
እናላችሁ… “አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው...” ከሚለው ‘ማስታወቂያ’ ጀርባ ያሉ ሰዎች የውጪ አገር ሰዎች ከሆኑ የለየላቸው ዘረኞች ናቸው፣ አበሾች ከሆኑ ‘ዘመናዊ እንቁላል ሻጮች’ ናቸው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ… ‘እንደ አሜሪካዊ ለመናገር’ በጉሮሯቸውና በአተነፋፈሳቸው ላይ ‘ሽብር የሚነዙ’ ሞልተውላቸኋል፡፡ አሀ… ስምንት ደብል ብርሌ በአርባ አምስት ደቂቃ ውስጥ የጠጣ ሰው እንኳን የእነሱ ያህል ፊደሎቹን አይፈረካክስም! እነኚህ አይነቶቹ ዋናው ግባቸው ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ‘የፈረንጅ አፍ’ ለማወቅ ሳይሆን ‘የፈረንጅ አፍ እንደሚያውቁ’ ሌላው እንዲያቅላቸው ነው፡፡ እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እንደው ዝም ብሎ “አድንቁኝ!” ምናምን ማለት አሪፍ አይደለም፡፡ ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ለራሱ ያለው አመለካከት ትንሽ የተጋነነ ነው፡፡ ታዲያላችሁ… አድናቆት ፍለጋ አንዱ ጓደኛውን “አንድ ሰው አንድ አህያን ሲደበድብ ባየውና አህያውን ባስጥለው ምን አይነት ፍቅር አሳየሁ ማለት ነው?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኛ ሆዬ ምን ብሎ መለሰለት መሰላችሁ… “ወንድማዊ ፍቅር!”
እናላችሁ… በግድ “አድንቁኝ!” አሪፍ አይደለም!
‘ጥጋብ’ እና ‘ዘመናዊነትን’ መለየት የሚያስችለውን ልቦና ይስጠንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ህብረተሰብ

           ገና በሃያ አምስት ዓመት ዕድሜዋ የስምንት ልጆች እናት መሆኗ ሁሌም ያበሣጫታል፡፡ በላይ በላይ እያከታተለች የምትወልዳቸውን ሕፃናት በአግባቡ ተንከባክቦ ማሣደግ ህልም ሆኖባታል፡፡ ባለቤቷ ችግሯን ሊጋራትና ሊደግፋት ፈፅሞ አይፈልግም፡፡ ይልቁንም መተዳደሪያቸው የሆነውን የእርሻ ሥራ ለመሥራት ከቤት በሚወጣበት ጊዜ ሁሉ ባለቤቱ እንድትከተለውና አረሙንም፣ ጉልጓሎውንም፣ ሰብል ስብሰባውንም እንድታግዘው ይፈልጋል፡፡ 
በሆዷና በጀርባዋ ልጆቿን ተሸክማ ማሣው ላይ ደፋ ቀና ስትል ውላ ትመለሳለች፡፡ ከዓመት ዓመት በሽታ እየተጫናትና አቅሟ እየደከመ መምጣቱም ይታወቃታል፡፡ እርግዝናና ወሊድ ተባብረው ጉልበቷን ነጥቀዋታል፡፡ ግን አማራጭ የላትም። ፈጣሪ በቃሽ እስኪላትና ወሊድ የምታቆምበት ተፈጥሯዊ ጊዜዋ እስኪደርስ በየዓመቱ መውለዷ እጣ ፈንታዋ እንደሆነ ታስባለች፡፡ ከዚህ ሥቃይና ችግር ሊገላግላት የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ አምና ተቀብላለች፡፡ ሴቶች ሳይፈልጉ ልጅ መውለድ እንዳይችሉ የሚያደርጋቸው መድሃኒት መኖሩን የወሬ ወሬ ብትሰማም፣ ነገሩን አምኖ መቀበሉ አልሆነላትም፡፡ የምትኖርበት ገጠራማው የአፈርደባ ቀበሌ፣ ለትራንስፖርት እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ነዋሪዎቹ ህክምናም ሆነ በጤና ተቋማት ውስጥ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን እንደልባቸው ለማግኘት አልታደሉም፡፡ በሐረሪ ክልል ሶፌ ወረዳ አፈርደባ ቀበሌ ውስጥ ያገኘኋት ይህቺው የስምንት ልጆች እናት፣ ትዳር ከመሰረተችበት የአስራ ስድስት ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ በየአመቱ እርግዝናና ወሊድን ለማስተናገድ ተገዳለች፡፡

ባለቤቷ አብዱራህማን ሠይድ፣ የልጆቹ ቁጥር ከአመት አመት እየጨመረና ኑሮ እየከበደው መምጣቱ ለአፍታም አሣስቦት አያውቅም፡፡ በሰበብ አስባቡ ከሚከሰተው ሞት ተርፈው ለፍሬ የሚበቁት ጥቂቶቹ ናቸውና የልጆቹን ቁጥር በየዓመቱ ለመጨመር እቅድ አለው፡፡ የባለቤቱ በእርግዝናና በወሊድ መጐዳት ለእሱ ትዝ አይለውም። ለሥራ ጉዳይ ወደ አካባቢው በሄድኩበት አንድ አጋጣሚ አግኝቼ ያነጋገርኳት ይህችው ሴት፣ ስለ ወሊድ መከላከያ በግልፅ አስረድቶ እንድትጠቀም ያበረታታት አንድም ሰው አለመኖሩን ነግራኛለች፡፡ በአካባቢያቸው ሴቶች በቡድን በቡድን እየተደራጁ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበትና የሚመክሩበት ሁኔታ እንዳለ ብትሰማም እሷ ወደዚህ ስብሰባና ውይይት እንድትሄድ ባሏ አይፈቅድላትም። እሷ ብቻ ሳትሆን ብዙዎቹ የአካባቢዋ ሴቶች የዚህ ስብሰባና ውይይት ተካፋዮች አይደሉም። እሷንና የእሷ መሰል እድል ያላቸውን ሴቶች ቤት ለቤት በሚደረግ አሠሣ በማግኘት ስለ ቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት፣ ስለ ቅድመ ወሊድና ድህረ ወሊድ፣ ስለ ህፃናት አስተዳደግና መሰል የጤና አገልግሎቶች ለማስተማርና ህብረተሰቡን ለመለወጥ የሚደረግ አንዳችም እንቅስቃሴ አለመኖሩንም ነግራኛለች። በአካባቢው የጤና ኬላና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ስለመኖራቸው እንኳን አታውቅም። የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞቹም ያለ ፍላጐቷ በየዓመቱ የአዳዲስ ህፃናት እናት ለመሆን የተፈረደባት ሴት መኖሯን አያውቁም፡፡
የዓለም አገራት እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም ለማሳካት ቃል ከገቡት የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች መካከል አንዱ የሆነው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በአገራችንም መሻሻሎችን እያሣየ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 ከነበረበት 15 በመቶ በ2011 ዓ.ም 29 በመቶ የደረሰ ሲሆን በተያዘለት የጊዜ ገደብ 66 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ መያዙ እየተነገረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ፈፅሞ የማያውቁ ሚሊዮኖች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ በዘርፉ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከ34ሺ የሚበልጡ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ሰልጥነው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሰማሩ ቢደረግም የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች የማይደርሱባቸውና ዛሬም ሳይፈልጉ በየዓመቱ የሚወልዱ እናቶች በርካቶች ናቸው፡፡
ባለሙያዎች ህብረተሰቡን ለማዳረስ እንዲሁም አስተማማኝና በጤናቸው ላይ ጉዳት ሊያስከትል የማይችል የወሊድ መቆጣጠሪያ ለመስጠት አሁንም የአቅም ውስንነት ችግር አለባቸው፡፡ የአገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ያለባቸው ምን አይነት ሴቶች እንደሆኑ፣ መጠቀም የሚገባቸው የትኛውን አይነት የእርግዝና መቆጣጠሪያ ዘዴ እንደሆነ ግልፅ ማብራሪያ በማግኘት ረገድ ችግር እንዳለባቸው ተጠቃሚዎቹ ይናገራሉ፡፡
ሰሞኑን በUSAID የሚደገፈውን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ለማየት ወደ ሻሸመኔ ከተማ ተጉዤ ነበር፡፡ አካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት እንደ ልብ የሚገኝበት እንደመሆኑ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉና ሌሎች ጤና ተቋማት የሚመጡ ነዋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደጉን የከተማው አስተዳደር ምክትል ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ውድነሽ ብሩ ይናገራሉ። በአካባቢው አንድ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ለአምስት መቶ ነዋሪዎች ተመድቦ ይሠራል፡፡ ይህ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር እንደሆነና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ ህብረተሰቡ ውስጥ በመግባት በአግባቡ ለማስተማርና የግንዛቤ ለውጥ ለማምጣት እንቅፋት እንደሚሆን በሥፍራው ያገኘናቸው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም የተደረገው የሥነ ህዝብ ጤና ጥናት እንደሚያመለክተው፣ 29 በመቶ የሚሆኑት በመውለጃ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች፣ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የቻሉ ሲሆን ይሄም እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም ከነበረው 15 በመቶ ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ መጨመሩን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል 25 በመቶ ያህሉ በመውለድ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች፣ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት መጠቀም ቢፈልጉም በተለያዩ ምክንያቶች ዕድሉን ለማግኘት እንዳልቻሉ ይኸው ጥናት ይጠቁማል፡፡
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት ሴቶች መካከልም አብዛኛዎቹ የአጭር ጊዜ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ይህንን ለማሻሻልም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የተለየ ትኩረት በመስጠት፣ ሴቶች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፊ ቅስቀሣ ያደርጋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም በክንድ ሥር የሚቀበር የወሊድ መከላከያ፣ በ2010 ደግሞ ሉፕ የተባለውን የወሊድ መከላከያ አገልግሎት ለህብረተሰቡ በስፋት ለማዳረስ ተንቀሳቅሷል፡፡
በጤናው ዘርፍ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ከሆኑት መካከል ያልተሟላ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ፍላጐትን ማሟላት አንዱ ነው፡፡ በዚህ መሠረትም የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሽፋኑን 66 በመቶ ለማድረስ እቅድ ተይዟል፡፡ ሆኖም በምዕተ ዓመቱ ይደረስበታል ተብሎ በዕቅድ የተያዘው ቁጥር ላይ መድረስ እንደማይቻልና አገሪቱ በዚህ ዘርፍ የተሳካ ዕድገት አለማስመዝገቧ ይነገራል፡፡ መንግስት ለቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ግብአት ለማሟላት የሚያስችል በጀት መድቦ መንቀሳቀስ የጀመረው እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ በፊት አገልግሎቱ ይሰጥ የነበረው በአጋር ድርጅቶች እርዳታና ድጋፍ ነበር፡፡
መንግስት እንቅስቃሴ በጀመረበት ዓመት፣ ከአገር ውስጥ ገቢ 910.000 ዶላር፣ ከጋራ ቋት ደግሞ 12 ሚሊዮን ዶላር መድቦ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን ይህም በየዓመቱ እየጨመረ በመሄድ ክልሎችም ለዚሁ አገልግሎት ከራሳቸው በጀት መመደብ ጀምረዋል፡፡
ለዚህ ዕቅድ እውን መሆን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች፣ የጐሣ መሪዎች፣ ማህበራት፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ መ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች ያልተቋረጠ ድጋፍና ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ባለፈው ማክሰኞ ተጀምሮ ትናንት በተጠናቀቀው 3ኛው አለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ጉባኤ ላይ ተገልጿል፡፡ “የተሟላ ምርጫ የተሟላ አቅርቦት” በሚል መሪ ቃል፣ ለአራት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ዓለም አቀፋዊ ጉባዔ ላይ ከ3ሺ በላይ ተሳታፊዎች የተካፈሉበት ሲሆን ከ100 በላይ የጥናት ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጐባቸዋል። “አገሪቱ በዘርፉ በምዕተ ዓመቱ ልታሳካው ያቀደችውን ማሳካት ይቻላት ይሆን?” የሚለው ጉዳይ ግን የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡

Published in ዋናው ጤና

22ሚ. ብር የሚፈጅ “የብዕር አምባ” ግንባታ ይጀመራል
አዲሱ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ መላው የአገሪቱ ደራሲያንና የድርሰት ወዳጆች ከስነ ጽሑፍ እድገት ጐን እንዲቆሙ ጠየቀ፡፡
በቅርቡ የተመረጠው የደራስያን ማህበር አመራር፤ ትላንት በፅ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ ማህበሩ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያካበተውን ልምድና ያከናወናቸውን ተግባራት መሠረት በማድረግ፣ ከዘመን ዘመን ማህበሩን ሲፈታተኑ የቆዩ ማነቆዎችንና ተግዳሮቶችን በማስወገድ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ አዳዲስ የአስተሳሰብና የአሠራር አቅጣጫዎችን ቀይሶ፣ አባላቱን ከዳር እስከዳር በማንቀሳቀስ ማህበሩን ወደ ላቀ የእድገት ደረጃ ለማድረስ ቆርጦ መነሣቱንም ገልጿል፡፡
የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ቀዳሚ የትኩረት እንቅስቃሴ አቅጣጫዎቼ ናቸው በማለት ከዘረዘራቸው መካከል፤ ከ22 ሚ. ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለው “የብዕር አምባ” ግንባታ እንዲጀመር ማድረግ፣ የማህበሩን ገቢ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማስፋትና የማህበሩን የህትመት ውጤቶች በብዛትም በጥራትም መጨመር የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በየክልሎቹ ያሉትን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ቁጥር ለማሳደግ እንደሚሠራና ብዕርተኞች የሚዘከሩባቸውን የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያካሂድ የገለፀው ማህበሩ፤ የመጽሐፍት ማከፋፈያና መሸጫ መደብሮች፣ በአዲስ አበባ ማዕከላዊ ቦታዎች ላይ ለመክፈት እጥራለሁ ብሏል፡፡ የማህበሩን ጥረት ለማገዝም የድርሰት ወዳጆች ከጐኑ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Published in ህብረተሰብ
Monday, 18 November 2013 10:59

የሁለት ደብዳቤዎች ወግ

የሰው ልጅ፤ ፈጣሪ ለክቶ በሰፈረለት የህይወት ዘመኑ ውስጥ እንደየእጣ ክፍሉ ከሚያጋጥሙት እጅግ የከፋ የመከራና የፈተና አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ስደት ነው፡፡ ስደት የሰውን ልጅ ከሰውነት ተራ ያስወጣል፡፡ ስደት የሰውን ልጅ ክቡር ስሙን ይነጥቃል፡፡ ስደት የሰውን ልጅ ከሰው ልጅነት ወደ ቁጥርነት ይለውጣል፡፡
ክቡር በሆነው የሰውነት ስማቸው ሳይሆን “ስደተኛ” በሚለው የወል ስማቸውና በየግል በተሰጣቸው ቁጥር ተለይተው የሚታወቁት ህዝቦች፣ ተወልደው ያደጉበትን፣ እትብታቸው የተቀበረበትን፣ ወግ ማዕረግ ያዩበትን ቀዬ ትተው እግራቸውን ወደተለያዩ አገራት በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የአረብ ሀገራት ለስደት ከነቀሉበት ቀን አንስቶ ስደተኝነታቸው ፍፃሜውን እስከሚያገኝበት ጊዜ ድረስ በቃል እንዲህ ነው ተብሎ የማይነገር እንግልት፣ መከራ፣ ስቃይና ስምና ክብር የሌለውን ሞት ተሸክመውት አብረው ይኖራሉ፡፡
ወደእነዚህ የአረብ ሀገራት በህገጥ መንገድ ከሚሰደዱት ውስጥ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ስደተኞች፤ ለቤተሰቦቻቸው ከሚልኩት ዶላር በፊት ቀድሞ የሚደርሰው አስከሬናቸው የታሸገበት ሳጥን እንደሆነ በአብዛኞቻችን ዘንድ በግልጽ የታወቀ ነው፡፡
ሳኡዲ አረቢያ ወደ ሀገሯ በህገወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞች ህጋዊ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ እንዲያወጡ ሰጥታው የነበረው የጊዜ ገደብ ባለፈው ሳምንት ተጠናቋል፡፡ ይህን ተከትሎም የደህንነትና የፖሊስ ሃይሏ ህጋዊ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ ባላወጡ ስደተኞች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ሰጥታለች፡፡ የደህንነትና የፖሊስ ሃይሏም በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በስደተኞቹ ላይ ዙሪያ መለስ እርምጃውን መውሰድ ጀምሯል፡፡ እናም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህገወጥ ስደተኞች ለሞት፤ ለእስርና ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል፡፡ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በሳኡዲ አረቢያ በስደት የሚኖሩ ልጆች ያሏቸውን ወላጆች ከወዲያ ወዲህ አራውጧቸዋል፡፡ ከእነዚህ ወላጆች መካከል በስደት ሳኡዲ አረቢያ ውስጥ የሚኖሩ ሴት ልጆች ያሏቸው ፊሊፒኒያዊትና ኢትዮጵያዊት እናት ከዚህ የሚከተለውን ደብዳቤአቸውን ጽፈው ወደ ሳኡዲ አረቢያ ልከዋል - ባለፈው ሳምንት ፡፡
ደብዳቤ አንድ
ለማቲልዳ ባንባንግ
ንጉስ አልሳውድ ጐዳና
ሪያድ ሳኡዲ አረቢያ
የተወደድሽው ልጅ ማቲልዳ፤ ይህን ደብዳቤ በሰላም እንደምታገኘው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በዚህ ደብዳቤ አማካኝነት አባትሽ ባንባንግ፣ ወንድሞችሽ ፖኩንና ሳሚ፣ ባጠቃላይ መላው ቤተሰቡ የናፍቆት ሰላምታቸውን ያቀርቡልሻል፡፡
ባለፈው ሳምንት ስልክ ደውለሽ በተነጋገርንበት ጊዜ እንደነገርኩሽ ሁሉ እኛ በጣም ደህና ነን፡፡ ሰሞኑን ሀገራችንን ከመታው ክፉ ሳይክሎን በክርስቶስና በእናቱ በድንገል ማርያም እርዳታ ተርፈናል፡፡ ሳይክሎኑ ባቅራቢያችን የሚገኙ ከተሞችን ጨርሶ ያልነበሩ ያህል አውድሞ የእኛን ከተማ ግን ሳይነካት ያለፈው በስላሴዎች ተአምር የተነሳ ነው፡፡
ልጄ ማቲልዳ - በሳኡዲ አረቢያ ስደተኞችን በተመለከተ የተነሳውን ግርግርና ፖሊሶች እየወሰዱት ያለውን እርምጃ በቴሌቪዥን እንዳየነው፣ በእውነቱ ስላንቺ ደህንነት ስጋት ገብቶን ነበር፡፡ በተለይ ሁለቱ ወንድሞችሽ ከቴሌቪዥኑ ላይ ተጣብቀው አልላቀቅ ብለው ነበር፡፡ ዜናው በሚቀርብበት በአንዱ ሰአት ላይ የሚያዩሽ ይመስላቸው ነበር፡፡ እነሱንም ሆነ እኔንና አባትሽን ገብቶን ከነበረው ከፍ ያለ ስጋት የገላገለን፣ ሁኔታው በተፈጠረ በማግስቱ የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውጭ ሀገር የፊሊፒንስ ሠራተኞች ጉዳይ ማስተባበሪያ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች የሰጡን ደህንነትሽን የሚያረጋግጥ መረጃ ነው፡፡ ወደ ሳኡዲ አረቢያ የላከሽ የውጭ ሀገር ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲውም ያለሽበትን ሁኔታና ደህንነትሽን የሚገልጽ ደብዳቤ በሶስተኛው ቀን ማለዳ ላይ ለአባትሽ እንዲደርሰው አድርጓል፡፡
መንግስት የፊሊፒንስ የቤት ሰራተኞች ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት በተለይ ደግሞ ወደ ሳኡዲ አረቢያ እንዳይሄዱ ካቻምና ከከለከለ ወዲህ፣ ቀደም ብላችሁ የሄዳችሁትን የእናንተን ወሬ ካለፈው ጊዜ በተሻለ እየተከታተለ መናገር ጀምሯል፡፡ የሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲውም የመንግስትን ቅጣት እየፈራም ቢሆን በሁለት ወር ግፋ ካለም በሶስት ወር አንዴ ስልክ እየደወለ ስለ ደህንነትሽ ያገኘውን ወሬ ያቀብለናል፡፡
ውዷ ማቲልዳ:- ባለፈው ጊዜ በፃፍሽልን ደብዳቤዎችሽም ሆነ በስልክ በተነጋገርን ቁጥር ስራ አግኝተሽ ወደ ሳኡዲ ከመሄድሽ በፊት በማሰልጠኛ ተቋሙ ውስጥ ገብተሽ ተገቢውን የሙያ ስልጠና መውሰድሽ፣ ዘመናዊ የቤት ውስጥ መገልገያ መሳሪያዎችን በሚገባና ያለ አንዳች ችግር መጠቀም እንዳስቻለሽ እንዲሁም የአረቦችን፣ የእስያንና የአውሮፓውያንን ምግቦች እንደ ፈለግሽው ከሽነሸ ማዘጋጀትሽን ስለነገርሽን እኔም ሆነ አባትሽ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ከዚህ በፊት አስረሽ የነበረችው ሴትዮና የባሏ እናት ባንቺ ተደስተው እንዲያ ይወዱሽ የነበረውም በዚህ ትምህርት ባገኘሽው ሙያ የተነሳ ነበር፡፡
ልጄ ማቲልዳ:- ከሙያ ስልጠናው ጐን ለጐን ለአጭር ጊዜ የወሰድሽውን የአረብኛ ቋንቋ ትምህርት በሚገባ በማዳበር ከአሰሪዎችሽ ጋር ሆነ ከተቀረው የአገሬው ዜጋ ጋር ያለችግር መግባባት በመቻልሽ በእውነቱ ልትደነቂ ይገባል፡፡ እሰየው! እንኳንም ወንድሞችሽ እንዳሾፉብሽ አልቀረሽ!
ማቲልዳዬ :- የባለፈውን ስራሽን ለቀሽ በተሻለ ደመወዝ አሁን ካለሽበት ቤት መቀጠርሽ በእውነቱ መልካም ነገር ነው፡፡ በወሰድሽው እርምጃ በተለይ አባትሽ፣ ወንድሞችሽን ልክ እንዳንቺ አስተዋይ መሆን እንዳለባቸው ጧትና ማታ ሲጨቀጭቃቸው ነበር፡፡
የሆኖ ሆኖ ግን መቸም ምስጋና ላንቺ ይሁንና፤ ታናናሽ ወንድሞችሽ ትምህርታቸውን በርትተው በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡ አባትሽም በከተማችን ከሚገኘው የህብረት ስራ ባንክ ትንሽ ገንዘብ ተበድሮ የተወሰኑ ማሽኖችን በመግዛት፣ የእንጨት ስራ ወርክሾፑን በመጠኑም ቢሆን ማስፋፋት ችሏል። ስራውም ቢሆን ምንም አይልም፡፡ ስላሴዎች ይመስገኑ፡፡
የተወደድሽው ማቲልዳ:- በየወሩ የምትልኪው ገንዘብ፣ ለወንድሞችሽ ትምህርት ቤት ከሚውለው አንድ መቶ ሰባት ዶላር በቀር፣ ቀሪው ስድስት መቶ ዶላር ወደ ሳኡዲ ከመሄድሽ በፊት አባትሽ በስምሽ በከፈተልሽ የባንክ አካውንት ውስጥ እየተቀመጠልሽ ይገኛል፡፡ የአሁኑን የስራ ኮንትራትሽን ከዘጠኝ ወር በኋላ ስትጨርሺ፣ በምንም አይነት ምክንያት ሳታመነቺ ወደ ሀገርሽና ወደ እኔ እናትሽ ቤት ተመለሽ። እኛም እኮ በጣም እጅግ በጣም ናፍቀንሻል፤ የአባትሽ ናፍቆትማ ይቅር አይነሳ! ነጋ ጠባ አንዴ ልጅ በህልሜ ስትታየኝ አደረች ይላል፡፡ አንዴ ደግሞ ልጄ ቀኑን ሙሉ በአይኔ ውል ስትለኝ ዋለች ይላል። የናፍቆቱ ነገር ምኑ ቅጡ፡፡ ብቻ ልጄ ኮንትራትሽን እንደጨረስሽ፣ ሳትውይ ሳታድሪ በቶሎ ተመለሺ፡፡ በሳኡዲ አረቢያ ስራ ይዘሽ ከሄድሽ ጊዜ ጀምሮ እየላክሽ የተጠራቀመልሽ ገንዘብ፣ ከልጅነትሽ ጀምሮ ትመኝው የነበረውን የዲያንግና ባትቾየ (በፊሊፒንስ ተወዳጅ የሆነ የአሳ ምግብና ሾርባ) ሬስቶራንት ለመክፈት በቂ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት ገንዘቡ የሚያንስሽ ከሆነም አባትሽ ከቁጠባ ማህበራቸው ሊበደርልሽ እንደሚችል ደጋግሞ ነግሮኛል፡፡
ማቲልዳዬ:- በይ እንግዲህ ደህና ሁኝ፡፡ እስክንገናኝ ድረስ የክርስቶስ እናት አትለይሽ፡፡ አክስትሽ ሚሸሊንና ባላ ጀኦል እንዲሁም አጐትሽ ሮዌ ሰላምታቸውን ያቀርቡልሻል፡፡
ደብዳቤ ሁለት
ይድረስ ለሃዋ ሰኢድ ሙሄ
ጅዳ - ሳኡዲ አረቢያ
ውድ ልጄ ሀዋ:- ከተለያየንበት ቀንና ሰአት አንስቶ ለጤናሽ እንደምን ትሆኛለሽ? እኔ አልሀምዱላሂ መቸም ከሞት ተርፌአለሁ፡፡ ሰሞኑን አገሩ በሞላ የሳኡዲ መንግስት አበሻውን ሙላ እየገደለ፣ እየደበደበና እያነቀ ዘብጥያ እየከተተ ነው እያለ ሞጥሮ ሲያወራ ስሰማ ጊዜ፣ አንቺን አንቆ እንዳይመልስሽ ብዬ ደንግጬ፣ ትንሽ ከሰሞኑ ሻል ብሎልኝ የነበረው በሽታ ከነጓዙ ጠቅልሎ አገረሸብኝ፡፡ አሁንማ እንጃልኝ እንዲያው እተርፍ ብለሽ ነው?
ውድ ልጄ ሀዋ:- የሳኡዲ መንግስት በዛ ሁላ የእኔ ቢጤ አበሻ ላይ እንዲህ ጨክኖ የተነሳው ምን ሆኖ ነው በይሳ? እንዲያው ምኑ ጂኒ ቢጠጋው ነው አንቺየ! ግን እንዲያው ለመሆኑ ያንቺሳ ነገር እንዴት ነው? ቦሊሶቹ አግኝተው አነቁሽ ወይስ እንዴት ነሽሳ! እኔማ ይህንን የሳኡዲ መንግስት በአበሻው ሁላ ተነሳ መባልን ስሰማ፣ እንዲያው አምርሬ አዝኘ ሳለቅስ ባጀሁ፡፡ ያለቀስኩትም የሚያስለቅሰኝም ሌላ ሳይሆን እድሌ ነው፡፡ ከድፍን ቤት ሙሉ ልጅ አንድ እንኳ ጧሪ ደጋፊ አለማውጣቴ ያስለቅሰኛል፡፡ የቀዬው ሰው ሁላ ቤት ሙሉ ልጅ ከመቀፍቀፍ በቀር ሌላ ሙያ የሌላት እያለ ነጋ ጠባ ያነውረኛል፡፡ የመሀመድ ኑር ይማም ሚስት እኮ ባቅሟ ከባሏ አፋታ ባህሬን የሰደደቻት ትልቋ ልጇ፣ በዚያው ሰሞን የሰደደችላትን ዘመን አመጣሽ ቀሚስ እየበተነች ስትወነንብኝ ትውላለች፡፡
ውድ ልጄ ሀዋ፤ ያን ጊዜ በየመን ከነራህመቶ ልጆች ጋር እንድትሄጂ ብዬ ለደላላው ያን ሁላ ገንዘብ አባትሽ የከፈለው፣ ጥማድ በሬውን ሽጦ እንደሆነ መቸም አታጭው፡፡ ከሄድሽ ጀምሮ ታዲያ እንደ ሰፈር ጓደኞችሽ እንኳን ዶላሩን ልትልኪ ቀርቶ መጋቢያሽንም እንዲህ ነው ሳትይ ስትቀሪ፣ አባትሽ ቅስሙ ተሰብሮ ወጀጅ ያረገው ጀምሮአል፡፡ እንኳን እንዳንቺ ያለው ልባም ይቅርና ስንቱ ገልቱ አልፎለት፣ ለናት አባቱ ዶላሩን እየላከ፣ አንቀባሮ በሚያሰልፍበት አገር፣ ያንቺ ነገር እንዲህ ሆኖ መቅረቱ ወላሂ በጣም ያሳዝናል፡፡ ለነገሩ ጠላቴ አንቺ ሳትሆኝ እድሌ ነው፡፡
ያንቺ ታላቅ ጓደኞቿን ተከትላ ስንት በረሃና ባህር አቋርጣ፣ ቤሩት ገብታ እየሰራችም ምንም እያለችም የምታገኛትን ለራሷ ሳትል ለእኛ እየላከች አንድ ሁለት አመት ደህና ቀጥ አድርጋ ይዛን ባጅታ ነበር፡፡ አባትሽም አምሮበት ደህና እንዲያው ሰው መስሎ ከርሞ ነበር፡፡ ግናስ የኔው ጠማማ እድል ተከትሏት፣ አሠሪ እመቤቷ በፈላ ውሃ ፊቷን ጠብሳ፣ መለመላዋን ስታባርራት ያገሩ ፖሊስም ለቀም አድርጐ ይዞ ጠርዞ ልኳት፣ የነፈረ አካሏን ይዛ ባዶ እጇን እያጨበጨበች መጣች፣ በኋላም “ሁለት አመት ሙሉ የላኩትን ገንዘብ ውለዱ” ብላ ቁም ስቅላችን ስታሳየን ኖራ፣ ዛሬ እዚህ ነኝ እንኳ ሳትለን የትሜናዋ ሄዳለች፡፡
አንቺዬ:- እንዲያው እኛ ቤት የገባው ሰይጣን ከቶ እንዴት ያለው ይሆን? የዚያች ያክስትሽ የአሻ መቁረጫ ልጇ ዘይነብ ብዙ ሳትከላተም፣ ባሬን ገባች ተብሎ ደስ ሲለነ ገና ሁለት ወር እንኳ ሳይሞላት፣ ያሰማችው ምጣድ በጀ አልል ብሏት፣ እሳቱ መላ አካላቷን ፈጅቷት ተብሎ፣ ሬሳዋ በሰንዱቅ ተጭኖ ለዚያች ከንቱ እናቷ መጣላት፡፡ የአባትሽ የወንድም ልጅ አሚናም እመቤቲቱ ሰይጣን ተጋብቷት፣ ከፎቅ ላይ ወርውራት ተብሎ ተጠርዛ መጥታ፣ እጅ እግሯ አይሰማ፣ ወገቧ አይላወስ፣ በድን ደንጊያ ሆና አለችው።
የሆነ ሆኖ ሃዋ:- እኔም ሆነ አባትሽ ተስፋችንን የጣልነው ባንቺ ላይ ነው፡፡ የሳኡዲው ቦሊስ አንቆ ጠርዞ እንዳይልክሽ፣ ቦሊሱ ባለበት መንደር እንጦለጦላለሁ ብለሽ ወት ወት እንዳትይ አደራ! እኔ እንደምታይኝ በበሽታ ተደይኜ ነው ያለሁ፡፡ አባትሽም ቢሆን እንዲያውም ነፍሱ ስላልወጣች እንጂ በጠና ተይዞ ነው ያለው፡፡
ወንድሞችሽና እህትቶችሽም ቢሆኑ ለትምህርት ቤት የሚከፍልላቸው ጠፍቶ፣ ይሄው የሰፈር አመድ ሲያቦሉ ይውላሉ፡፡ አያትሽ አያ ሙሄም በራብ የተወጋ ጐኑ እንዲያው አንድ ቀን እንኳ ቀና ሳይል፣ በባዶ ቤት እየተቆራመደ ይኖራል። እንዲያው አንደዜ እንኳ እጅሽን ሳትዘረጊለት ድፍት ብሎ ቢቀር ኋላ ይቆጭሻል፡፡
እና አሁንም የሆነ እንደሆነ ተጠርዞ ከሚመጣው አንድ አገር አበሻ የኛ አገር ልጅ፣ ተኛ ወገን የሆነውን ፈልጊና ዶላሩን ላኪልነ፡፡ አደራ በሰማይ አደራ በምድር በምድር! ኋላ እንዲችው ተቆራምደን “አዬ የልጅ ያለህ” እንዳልን፣ እኔም ሆነ አባትሽ ወንድምና እህቶችሽን ባዶ ቤት በትነን ብንሞት ይቆጭሻል፡፡
ያኔ አባቴ አባቴ ብትይ፣ እናቴ እናቴ እያልሽ ወዮ እላለሁ ብትይ ቀየውም፣ አድባሩም አያቆምሽ! እንግዲህ የዶላሩን ነገር አደራ! በሰማይ አደራ በምድር ብዬሻለሁ፡፡
ውድ እናትሽ፤ ሰይዳ ከድር

Published in ህብረተሰብ

                             ሰውዬው ጢማቸውን ማሳደግና ዘወትር ማለዳ ተነስተው እርጐ መጐንጨት ያዘወትራሉ፡፡ ታዲያ ማለዳ ማለዳ እርጐውን ተጐንጭተውና አጣጥመው እንደጨረሱ አፋቸውን ሲጉመጠመጡ፣ ከላይኛው የከንፈራቸው ጢም ውስጥ ሰርገው የሚቀሩትን የእርጐ ፍንጣቂዎች ይረሷቸዋል፡፡ ከአፍንጫቸው ሥራ የተረሱት እነዚያ የእርጐ ፍንጣቂዎች መዋል ማደር ሲጀምሩ ጠረናቸው እየተለወጠ የሚፈጥሩት ሽታ ጤና ነሳቸው፡፡ አንድ ቀን ማለዳ ላይ ባለቤታቸውን፡- 
“እዚህ ቤት የሞተ ዐይጥ አለ እንዴ?”
“ከመቼ ወዲህ አንቱዬ?”
“ታዲያ የሚሸተኝ ምንድን ነው? … የለ … የለም እዚህ ቤት የሞተ ዐይጥ አለ! ያውም የከረመ! … በይ የቤቱን ዕቃ በሙሉ እያወጣሽ ቤቱን አፅጂው!” ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡
“ካሉ ደግ አፀደዋለሁ”
“በይ አሁኑኑ ጀምሪ! እስተዚያው እኔም ዘወር ዘወር ብዬ ልምጣ!” ሰውየው ምላሽ ሳይጠብቁ ከዘራቸውን አንስተው ይወጣሉ፡፡ ነገር ግን ሰውዬው በየሄዱበት ቦታ ሁሉ ያ መጥፎ ጠረን ይከተላቸው ጀመር፡፡ እዚያ ቢሄዱ እዚህ ቢመጡም ያው ሆነባቸው፤ ወደቤታቸው እያዘገሙ ሳለ ሰውዬው እንዲህ አሉ፡- “ዛሬስ የኔ ቤት ብቻ አይደለም፤ አገሩ ሁሉ ገምቷል!”
                                                      * * *
የአንድ ዘመን ማሕበረሰብ ባህል፣ አስተሳሰብና የሚከተለው የፖለቲካ ሥርዓት በየግለሰቡ መልካም ስብዕና ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል፡፡ በእያንዳንዱ ግለሰብ መልካም ስብዕና ላይ የየዘመኑ ሥርዓት የሚፈጥረው ዕድፍ እየተለመደ፣ ከእያንዳንዱ ማንነት ጋር ሲዋሀድ ያኔ ብክለቱ ይጀምራል፡፡ ይህን በተመለከተ የፖለቲካ ሳይንሱ ምሁር ካርል ማርክስ ሲናገር፡-
“አንድን ሥርዓት ለመጣል ሃያና ሰላሳ ዓመታት መታገል ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከሥርዓቱ ዕድፍ ለመላቀቅ መቶና ከዚያም በላይ ዓመታት መታገል ያስፈልጋል፡፡”
ትናንት ከትናንት በስቲያና ዛሬ በኛ ማሕበረሰብ ውስጥ የተቀያየሩ የፖለቲካ ሥርዓቶች ያሸከሙን ዕድፍ ጠባሳው ሳይሽር ቁስሉ እያመረቀዘ አላራምድ ብሎናል፡፡ ትናንት ያረፈብን ዱላ ዛሬ ቀና ብለን እንዳንራመድ አስጐንብሶናል፡፡ የኛ ማሕበረሰብ የፖለቲካ ሥርዓቶች ያሸከሙን ዕዳ ምን ይመስላል?
የትናንት በስቲያው
በአንድ አጋጣሚ ከአንድ ወጣት ጋር ተገናኝተን ስናወጋ ያጫወተኝን ላካፍላችሁ ወደድሁ፡፡ የግል ሕይወቱን በተመለከተ እንዲህ ነበር ያወጋኝ፡፡
“አራት ወንድሞቼና ሁለት እህቶቼን ጨምሮ ከእናታችን ጋር ስምንት ሆነን ቀበሌ በሰጠን አንድ ክፍል ቤት ውስጥ እንኖራለን፡፡ አባታችን ወታደር ነበር፡፡ በሰሜኑ ጦር ግንባር ለረዥም ጊዜ ቆይቷል። ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎች ሲመለሱ የኛም አባት ይመለስ ይሆናል እያልን በተስፋ በር በሩን እያየን ስንጠብቅ ከረምን፡፡ እስከ አሁን ድረስ በሕይወት ይኑር ወይ ይሙት የምናውቀው ነገር የለም፡፡ እማዬ እንጀራና አምባሻ እየሸጠች ነው የምታስተዳድረን፡፡ ያገኘነውን ተካፍለን ከጠፋም ቆሎ ቆርጥመን እናድራለን፡፡ እኔና ታናሽ እህቴ 12ኛ ክፍል ጨርሰናል፡፡ ውጤት ግን አልመጣልንም፡፡ የሁሉም ታላቅ እኔ በመሆኔ የእማዬን ድካም እያየሁ በዝምታ መቀመጥ አልቻልኩም፡፡ እንደምንም ተሯሩጬ ታናሽ እህቴን ኬክ ቤት አስቀጠርኳት፡፡”
“አንተስ?” አልኩት ንግግሩን አቋርጬ
“ሥራ ለማግኘት ብዙ ጣርኩ፡፡ አልተሳካልኝም ነበር፡፡ የኋላ ኋላ በአንድ የእንጨት ሥራ ድርጅት ውስጥ ሥራ አገኘሁ፡፡ ተመስገን ብዬ ሥራ ጀመርኩ። ከሶስት ወር በኋላ ግን ድርጅቱ ተዘጋ፡፡”
“ለምን?”
“የድርጅቱ ባለቤት ከሰርኩ አለ”
“ከዚያስ ሌላ ቦታ አልሞከርክም?”
“ለብዙ ጊዜ ሥራዬ ሥራ መፈለግ ብቻ ሆነ። ነገር ግን አልቻልኩም፡፡ አንድ ቀን ቁጭ ብዬ ሳሰላስል በአካባቢዬ የማያቸው የጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጆች ለሥራ ያላቸው ታታሪነት ታሰበኝ፡፡ ሥራ ሳይንቁ ሊስትሮ ሆነው ይጀምሩና ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሱቅ ከፍተው ታገኛቸዋለህ፡፡ እኔስ ለምን በሊስትሮነት አልጀምርም? ብዬ አሰብኩኝ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ራሴን ብችል እማዬን አገዝኳት ማለት ነው፡፡ ታናሽ እህቴ ኬክ ቤት ትሠራለች ብዬሃለሁ፡፡”
“እኔ ራሴን ከቻልኩ ለእማዬ ሁለት ሆድ ተቀነሰላት ማለት ነው”
በአነጋገሩ ፈገግ አልኩ፡፡
“የሊስትሮነት ሥራዬን ለመጀመር ግን የሠፈሬን ሰዎችና የጓደኞቼን ሽሙጥ በመፍራት ብዙ አቅማማሁ፡፡ የኋላ ኋላ ስለ እማዬ ሳስብ ቶሎ ለመጀመር ወሰንኩ”
“ስለ እማዬ ሳስብ ነው ያልከኝ?”
“አዎና! እማዬ ድንገት አንድ ነገር ብትሆን፣ ብትታመምብኝ ወይም አያድርገውና ብትሞትብኝ ፀፀቱን አልችለውም ብዬ ጫማ መስፋት ስለምችል፣ ከሊስትሮ ሥራ ጋር ደርቤ እዚያው ከሠፈራችን ጀመርኩ፡፡”
“እንዴት ነው ተሳካልህ?” አልኩት ጥንካሬውን እያደነቅሁ
“ምን ይሳካል ብለህ … በሁለተኛው ቀን ተቋረጠ።”
“ለምን?”
“ሥራውን እንደጀመርኩ በሁለተኛው ቀን እማዬ እየተንደረደረች መጣችና፡-
“አንተ የማትረባ! ብለህ ብለህ ተከብሬ በኖርኩበት ሠፈር ልታዋርደኝ ተነሳህ? … ይኸው ነው የቀረህ! … ምንም ብደኸይ … ምንም ጊዜ ቢጥለኝ … እ … የነማን ዘር መሰልኩህ! አንተ ዘር አሰዳቢ! … የፅጌ ልጅ ሊስትሮ ሆነ ብሎ አገር እንዲስቅብኝ ነው? … ቆሜ ነው ሞቼ!”
“እማዬ እንደዚያን ዕለት በንዴት ስትቃጠል አይቻት አላውቅም፡፡ የሊስትሮ ሳጥኔን ሰባበረቺውና አምባሻ ጋገረችበት እልሃለሁ! … አይ እማዬ በዚያች የሊስትሮ ሳጥን ስባሪ ስንት አምባሻ ጋግራበት ይሆን?” አለኝ ፈገግ ብሎ፡፡ ፈገግታውን አልተጋራሁትም፡፡
የትናንትናውስ?
ያኔ … የሰለሞናዊው ዘውድ ሥርዓት ማክተሚያ ሲቃረብ፣ ዳር እስከዳር የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ አመፅና የተማሪዎች የለውጥ ትግል ተጠቅሞ ወታደራዊው ደርግ በትረ-ሙሴውን ጨበጠ። ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እስከሚቋቋም በጊዜያዊነት የሥልጣን መንበር ላይ የወጣው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት፤ “የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ክፍል የለም” በሚል ሰበብ የጣመውን የሥልጣኝ መንበር ቀስ በቀስ እያመቻቸ መሠረቱን ማጠናከር ያዘ፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል መፈክር መሪነት፡፡ “ያለምንም ደም እንከኗ ይውደም በቆራጥ ልጆቿ ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል ዜማ፣ የለውጥ ፈላጊውን ስሜት ሊያረግብ ጣረ፡፡ በወቅቱ የነበረው ወጣት ትውልድ፣ በራሱ የሚተማመን ነበርና ይህን ወታደራዊ ብልጠት በዝምታ ሊያልፈው አልፈቀደም፡፡ አመፃቸውን ቀጠሉ፡፡ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ!” እያሉ ጮኹ። ወታደራዊው መንግሥት እየጣፈጠው የመጣውን ሥልጣን ላለመነጠቅ ፈራ፡፡
መሠረታዊው ማንነቱና ሥልጣን ያለ መነጠቅ ፍላጐቱ ፍራቻን አስከትሎ ጭካኔን ወለደ፡፡ “ያለ ምንም ደም” የሚለው ዜማ ቀረና ስልሳዎቹን የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት
“የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች
ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች፡፡”
አስተጋባ፡፡
የያኔዎቹ ወጣቶች ለማስፈራሪያው ዜማ አልተበገሩም፡፡ ወታደራዊው መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ በአቋማቸው ፀንተው ጮኹ። ወታደራዊው መንግሥት ያነገበውን መሣሪያ በማውረድ አፈ ሙዙን በወጣቶቹ ላይ ደገነ፡፡ ፍርሃቱ ጭካኔን ወለደ፡፡
ወጣቶቹም ወኔያቸውን አንግበው ከተደገነባቸው አፈ ሙዝ ፊት ለፊት በጽናት ቆሙ፡፡ በእኒያ ወጣቶች ደረት ላይ የተወደረው አፈ ሙዝ በጭካኔ ተሳበ፡፡ ጥይት በወጣቶቹ ላይ በጭካኔ ተርከፈከፈ፡፡ የምድረ ኢትዮጵያ ወጣት ታደነ፡፡ እሥር ቤቶች ተጣበቡ። የየቀበሌ ጽ/ቤቶች ወደ እሥር ቤት ተለወጡ፡፡ ግርፋትና ስቃይ በረከተ፡፡ የብዙ ሺህ ወጣቶች ሬሣ በየአውራ ጐዳናው፣ በአደባባዩና በየጢሻው እንደ ውሻ ሬሣ ተጣለ፡፡
በነዚያ ወጣቶች ላይ ፍርሃት በወለደው ጭካኔ የተዘራው ጥይት ለቀሩት ኢትዮጵያውያን ልጓም ሆነ፡፡ ጥርጣሬና ፍርሃት ነገሰ፡፡ በራስ መተማመን ጠፋ፡፡ ጠቢባን በቡርሻቸውም ሆነ በብዕራቸው ፈሩ፡፡ ፍርሃታቸው ማስመሰላቸውን እንደ ብልጠት ይቆጥሩት ዘንድ አስመረጣቸው፡፡ የመረጡትንም ተካኑበት፡፡
ይህን ጊዜ አዕምሮ ዛገ፡፡ እጆች ዛሉ፡፡ ጣቶችም ዶለዶሙ፡፡ ዐይኖች ወደ ውስጥ ማየታቸውን አቆሙ፡፡ ጆሮ ብቻ ዳባ አልለብስም አለ፡፡ ብዕር ማስመሰሉን አነባ…ጥበብ ወገቧ እስኪለመጥ ድረስ በሀዘን አቀረቀረች፡፡ እውነት ወዴት ነሽ? ውበት የት አለሽ? ከቶም ያለ የለም፡፡ ታዳጊዎች፤ ታላላቆቻቸው በብዕራቸውም በቡርሻቸውም በስብዕናቸውም ሲያስመስሉ አስተዋሉ፡፡ እያስተዋሉም ወደወጣትነት ተሸጋገሩ፡፡ አኢወማ ዘምሩ ሲላቸው ዘመሩ፡፡ መፈክር አሰሙ ሲላቸው በመሽቀዳደም ግራ እጃቸውን እያወጡ ፎከሩ፡፡
“ከመምሕሩ ደቀ መዝሙሩ” እንዲሉ ከታላላቆቻው እጥፍ ፈሪዎች፣ እጥፍ አስመሳዮች ሆኑ፡፡ ብሔራዊ ውትድርና መጣ፡፡ ሽሽት ተከተለ። ቤት ዘግቶ መደበቅ፤ ከአሁን አሁን ተያዝኩ የሚል ሥጋት አየለ፡፡ የእያንዳንዱ ወጣት ልብ ሥጋት እያባነነው፣ የፍርሃት ከበሮውን መደለቅ ተያያዘ። ታላላቆቻቸውን ጉራማይሌ ተነቀሱ፡፡ ከፈሩት ታላላቆቻቸው መቶ እጥፍ እየፈሩ፣ ከኒያ ፀንተው ከወደቁት ታላላቆቻቸው የወረሷት ትንሽዬ በራስ መተማመን ከፍርሃት ትንፋሻቸው ጋር እየተነፈሷት ብን ብላ ትጠፋባቸው ጀመር፡፡
ይህን ጊዜ ከፊሉ በአኢወማ ዙሪያ ማስመሰሉን ተካነበት፡፡ ከፊሉም ስደትን መረጠ፡፡ ጥቂቱም ሕይወቱን በዘዴ ለማክረም ውትድርና ተቀጠረ። በለስ ያልቀናው ብሔራዊ ውትድርና ዘመተ፡፡ ብዙዎቹ የሞት ገፈት ቀማሾች ሆኑ፡፡ የሞተውም ሞተ፡፡ የተረፈውም ሙት ደመ ነብሱ እየመራው፣ ከፍርሃቱና ከማስመሰሉ ጋር መወዛወዙን ቀጠለ፡፡
ሥፍራው ቢለያይም እኔና እናንተ ከእነሱ ጋር አለን፤ አሊያም የእነሱ ልጆች ነን፡፡
ትናንት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራርና አባላት የነበሩ ዛሬ ባሕር ማዶ ሆነው በሚያሳትሟቸው መፃሕፍት የሚያስነብቡን ትረካ፣ የትዝታ ድንኳን ጥለው ትናንትናቸውን እያለቀሱ፣ የኛን ዛሬ ሀዘንተኛ አድርገዋት፣ ነጠላዋን ካዘቀዘቀች’ኮ ከራረመች፡፡
ሁሉም “ትክክል ነበርኩ” እያለ በትዝታ የተወልን ሽንፈት፣ ትሩፋቱ ለቅሶ ብቻ ሆነ፡፡ የሀገራችን የትግል ታሪክ መቋጫው ምባ ብቻ ነው፤ በልቅሶ የተሞሸረ ሽንፈት፡፡ አቤት የዚች ምድር ለቅሶ! አቤት የዚች ምድር እምባ መብዛቱ! ዛሬም ድህነት ቅነሳ፣ ሙስና፣ የአመለካከት ለውጥ፣ ረሃብና ድርቅ በየመድረኩ ላይ አጀንዳ እየቀያየረ በባዶ አንጀታችን እናለቅሳለን። ያላየው ድርቅ ያልጐበኘው እምባችንን ብቻ ነው። ለቅሶ በኛ መንደር፣ ልቅሶ በኛ ቀዬ፣ ለቅሶ በኛ አደባባይ በሽበሽ ነው? የሰቀቀን ለቅሶ የሚያበቃበት ቀን እየናፈቀን በናፍቆት መኖሩ ተስፋ ሆነን እንዴ ጐበዝ? እንባችንን የምናብስበት የተስፋ መሀረብ ከቶ ከየት ይገኝ ይሆን?
አጋጣሚ ከሚያገጣጥመኝ የዘመኔ ዘመነኞች መሃል ጥቂት የማይባሉት “ነፋስ ሲነፍስ ጐንበስ ብሎ ማሳለፍን ከሣር ተማር!” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር አዘውትረው ሲናገሩ ሰማሁና፤
“ለምን?” ስላቸው
“መስለህ መኖር ካልቻልክ አከተመልህ ለመኖር ትንሽ ብልጥ መሆን አለብህ፤ ምስማሩን አሊያም መዶሻውን መሆን ያንተ ምርጫ ነው፤ ሲያዙህ እሺ አሜን እያልክ እንደሰው አምሮብህ ከሰው ሳታንስ መኖር ከቻልክ ሌላ ምን ትፈልጋለህ? ከጊዜው ጋር ተስማምቶ መኖር ብልጠትም ዕውቀትም ነው” አሉኝ፡፡
ምሳሌያዊ አነጋገር ከፍላጐት ጋር ተጣረሰ። አድርባይነት እንደ ብልጠትም ዕውቀትም ተቆጥሮ ብዙዎችን “ዐዋቂ” አሰኘ፡፡ ብዙዎች አድር ባይነታቸውን እንደ ብልጠት እየቆጠሩ፣ ህሊናቸው ላይ ተኝተው በብልጠታቸው ተኮፈሱ፡፡ አስመሳይነታቸው የኩራታቸው ምንጭ ሆነ፡፡
አንድ ወጣት ገጣሚ የቋጠረው ስንኝ ነብሴን ማርኮታል :-
“ሰውማ ሙዝ ሆና ተልጦ ቢበላ”
ውስጡ በተጣለ ላዩ በተበላ
ሰው እንደ ሙዝ ተልጦ ባይበላም የኔ ዘመን ዘመነኞች ግን አበላሉን ተክነውበታል! በአስመሳይ ክህሎቱ አንዱ አንደኛውን እንደ ሙዝ ሳይልጠው እርስ በርስ ይበላላ ይዟል፡፡ ያውም የሚጣለውንና የሚበላውን ሳይለይ፣ መብላቱን ወይም መበላቱን አሊያም መጣሉን ሳያውቅ ደመ ነብሱ እየመራው፣ በሆዱ ለሆዱ ስለሆዱ ብቻ መኖር መረጠ፡፡ የመረጠውንም እንደ ብልጠት ቆጠረው፡፡
ሁሉም ለሆዱ በሆዱ ሲጋፋ ህሊናውን ረሳ። የተጣለበትን ኃላፊነት ወደ ጐን በመተው ሰርቆና ዘርፎ አሊያም ዕምነት አጉድሎ ሀብታም ለመሆን መጣደፍ እንደ ጀብድ ተቆጥሮ ያስከብር ጀመር። ህሊናውን ሲረሳ ሰው የመሆኑን ክብር ከእግሮቹ ሥር ጣለና ራሱን በራሱ አቀለለ፤ ሰው ማለት ለሰው እንደገለባ ቀለለ፡፡ የሆዱን ሲያሳድድ አንዱ ላንዱ አልታኘከው እያለ እንደ አንጆ ሥጋ እርስ በርስ መጣጣል ተለመደ፡፡ ህሊና ረከሰ፤ ሥጋ ተወደደ፡፡
አንድ ኪሎ ሥጋ መቶ ስልሳ፤ መቶ ሰማኒያ ይሸጣል፤ ይቸበቸባል!
ሰው ዋጋ አላወጣም፡፡ ሰሞኑን የወጣና ሲኒማ አምፒየር በመታየት ላይ ያለው “ድሮና ዘንድሮ” የሚለው ፊልም “ሎጐ” እንዲህ ይላል:- “ከማትረባ ነብስ ድፍን መቶ ብር ሲጠፋ ያንገበግባል” ለመሆኑ የሰው ዋጋው ስንት ነው?
ልብ በሉ! እኔ በእናንተ ውስጥ አለሁ፡፡
የዘመኔ ዘመነኞች ሆይ፤ ማንነታችንን የሚያረክስና ስብዕናችንን የሚያዋረድ ዝቃጭ የሥርዓት ዕድፍ ተሸክመን እያለ…በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቃ፣ ጉስቁልናዋ በዝቶ፣ የሰቆቃ ሲቃዋ ሰቀቀን ሆኖባት፣ ሀዘኗ ልክ አጥቶ የደም ዕምባዋን በምትናጥ ሀገረ ኢትዮጵያ፣ በዚች ምድረ ሀበሻ፣ መልካም ስብዕና ያለው ታታሪ ዜጋ ተፈጥሮ፣ ሀገራችን በዕድገቷ ሽቅብ ተመንጥቃ ለማየት መመኘት ይቻላል፤ ምኞት አይከለከልምና! ነገር ግን ይህ ምኞት “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉ ከግብራችን ጋር ያልተዋሀደ ከንቱ ምኞት ነው፡፡
እያንዳንዳችን ከተሸከምነው የሥርዓት ዕድፍ ራሳችንን ለማላቀቅ፣ ከራሳችን ጋር ግብግብ እንግጠም፡፡ በመጀመሪያ ከየራሳችን ማንነት ጋር መታገል እንጀምር፡፡ ይህን ስናደርግ እንደ አንድ ማህበረሰብ በኛ ራስ ወዳድነት የተበከለውን የዘመናችንን አየር ለማጽዳት አንድ እርምጃ ተራመድን ማለት ነው፡፡
አጀንዳ ሳንጨርስ፣ በዐውደ ጥናት ሰበብ የሕዝብ ገንዘብ ሳይባክን፣ የአመለካከት ለውጥ እውን የሚሆንበት ጅማሮ የሚታየውም ይህን ጊዜ ነው፡፡ መራሩን መድኃኒት ስንወስድ፣ ከራስ ማንነት ጋር ትግል ስንጀምር! ነገር ግን ዛሬ በአንድ ጊዜ ከየራሳችን ማንነት ጋር ትግል ብንጀምር እያንዳንዳችን የተሸከምነው ዕድፍ ተራግፎልን በራሱ የሚተማመን ትውልድ በኛ ሕብረተሰብ መሃል ዛሬውኑ አይፈጠርልንም፡፡ ይህን የምንጠብቅ ከሆነ ተሳስተናል፡፡ እኛ ችግኝ ተካዮች እንጂ ፍሬውን ተቋዳሽ አለመሆናችንን እንመን፡፡
የዘመኔ ዘመነኞች ሆይ፤ በዘመናችን የተከሰቱ ሥርዓቶች ያሸከሙን ዕድፍ መጥፎ ጠረን የዘመናችንን አየር በክሎታል፡፡ የመልካም ስብዕና፣ በራስ የመተማመን አየር አጥሮን ቁና ቁና እየተነፈስን፣ የአመለካከት ለውጥ እያልን በሚቆራረጥ ድምጽ መቃተት ጀምረናል፡፡ የሚያሸት አፍንጫ ካለን፡፡ ከህመማችን የሚፈውሰን ፍቱን መድኃኒት በእጃችን ውስጥ እያለ በዘመናችን መንገድ ላይ ማስመሰላችንን ተንተርሰን፣ በራስ ወዳድነት ቃሬዛ ላይ እንደተኛን በለመድነው ማስመስል “የሀኪም ያለህ” እያልን ማቃሰት ይዘናል፡፡ የመድኃኒቱ ፈዋሽነት አሊያም አጠቃቀሙ የጠፋብን አሳዛኝ የዘመን በሽተኞች! ከፊሎቻችን የመድኃኒቱ ፈዋሽነትና አወሳሰዱ ሳይጠፋብን፣ የመድኃኒቱን መራርነት ፈርተን ነው በማስመሰል “የሃኪም ያለህ” እያልን አማራጭ ፍለጋ ዘመናችንን የምናቃስተው፡፡ ዞሮ ዞሮ መድኃኒት የሚያስፈልገን በሽተኞች መሆናችን አያጠያይቅም፡፡
በየዕለቱ የሚወሰድና ለዓመታት የማያቋርጥ መራር መድኃኒት፣ ከማንም በላይ ከምንወደው ከራሳችን ማንነት ጋር መታገል ነው፡፡ ከእሬት የመረረ ቢሆንም ከጽኑ በሽታችን የሚፈውሰን መድኃኒት እሱ ነው፡፡
የዛሬው ቁስላችንን ሳይሆን የትናንት ጠባሳችንን በትዝታ እየታመምን፣ ዛሬን ዛሬን የምናለቅስበት እኛ፤ ከዛሬው ህመማችን ባሻገር የመልካምነታችን ንጋት ተስፋው እየታየን፣ በዘመናችን የምንደሰተው መቼ ይሆን?
የትውልድ ቀጣይነታችን ወንዙ በዘመን ሸለቆ ውስጥ ስለሌለ ሳይሆን፣ በራስ ወዳድነት ለቅሶ የዕምባ ጅረት እየሰራ ቁልቁል የመፍሰሱ ማክተሚያ መቼ ይሆን? የዘመናችን ውቅያኖስ በራስ ወዳድነታችን ሞገድ ተናውጧልና ባህሩ ፀጥ እንዲል ከዘመናችን መርከብ ላይ የምትወረውረው ዮናስ የት ነህ?
የዘመኔ ዘመነኞች ሆይ፤ ምጤ እናንተ ናችሁና… እናንተን እጮኻለሁ!
በእኔ ውስጥ ስላላችሁ እናንተን እጮኻለሁ!
ሰው መሆናችንን እያለምኩ እኛን እጮኻለሁ!
ጆሮዎቻችሁ ወደ ድምጼ አቅጣጫ ተቀስረው ጩኸቴን እስክታዳምጡ ድረስ እጮኻለሁ!
ሀዘኔን የሚያስረሳ፣ ሕልሜን ዕውን አድርጐ ተስፋዬን የሚያለመልም ድምጽ እስክሰማ ድረስ የዘመን ንቅሣቴን እጮኻለሁ!
“ሕይወት ከባድ ነች፤ የበጐች መንጋ የውሾች ግትልትል አይደለችም፡፡
እያንዳንዱ ውሻ ግን እንደየድምፁ ይጮኻል”
ማክሲም ጐርኪይ

Published in ህብረተሰብ
Page 10 of 19