ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 200 ሚ.ብር ይፈጃል
ለባህሬን የምትሮጠው አትሌት ማርያም የሱፍ ጀማልና ባለቤቷ አቶ ወንድወሰን ዲሶ (ታረቅ) በአዲስ አበባ ከተማ መገናኛ አካባቢ፣ ከዳያስፖራ አደባባይ ፊት ለፊት ዳገቱ ላይ ያሠሩት ዘመናዊ ባለ “4 ኮከቡ” ቤላ ቪው ሆቴልና ስፓ ዛሬ ይመረቃል፡፡
የቬላ ቪው ሆቴልና ስፓ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ ሆቴሉ 35 ክፍሎችና ስፓ ሲኖረው፣ ስፓው በውበትና በትልቅነት በመዲናችን ብቻ ሳይሆን በአገራችንም የመጀመሪያው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በ “ሶፍ ኦማር” የተሰየሙ ስፓ፣ አዋሽ ሳውናና ስቲም፣ ዳሎል ጃኩዚ ትክክለኛው ሞሮኮ ባዝ፣ የእጅ፣ የእግርና የጥፍር መዋቢያ፣ የሴቶችና የወንዶች ፀጉር ቤት፣ ቦብ ማርሌ የፊት ማስዋቢያ እንዲሁም በላሊበላ፣ አክሱም፣ ፋሲለደስና ኮንሶ የተሰየሙ የማሳጅ ክፍሎች እንዳሉት ሥራ አስኪያጁ አብራርቷል፡፡
ሆቴሉ ላይ ሆኖ አዲስ አበባን መመልከት ልብ ይማርካል ያለው ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ከጀርባ ያለው ተራራ ፈረንሳይ ሌጋሲዮንን ከመጋረዱ በስተቀር በሁሉም አቅጣጫ ከተማዋን ፍንትው አድርጐ በማሳየት፣ በከተማዋ ካሉ ሆቴሎች ሁሉ ይልቃል ብሏል፡፡ ቬላ ቪው በፈረንሳይኛ “ጥሩ፣ ውብ፣ ቆንጆ፣ እይታ” ማለት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ባለ ስንት ኮከብ እንደሆነ ተጠይቆ ባለቤቱ ሲመልሱ፣ ከሆቴልና ቱሪዝም ሚ/ር የመጡ ባለሙያዎች ሆቴሉ ያሉትን ፋሲሊቲዎች ካዩ በኋላ፣4 ኮከብ ሊያሟላ እንደሚችል አረጋግጠው፣ “ከፈለጋችሁ 5 ኮከብ ጠይቁ” እንዳሏቸው ተናግሯል፡፡ ሆቴሉ የመዋኛ ገንዳና ከቤት ውጭ ስፖርቶች ማካሄጃ ቢኖረው፣ ባለ 5 ኮከብ ደረጃ ሊያሟላ እንደሚችል ጠቅሶ፣ መጀመሪያውኑ ዕቅዳቸው ባለ 4 ኮከብ ስለሆነ፣ በዚሁ ደረጃ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት እንደሚቀጥሉ ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ እንዳለ ሆኖ፣ ሆቴሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የስዊስ፣ የፈረንሳይና የጣሊያን ምግብ እንደሚያዘጋጅ የገለፀው አቶ ወንድወሰን፣ ለዚህም በፓሪስ ሂልተንና በሌሎች ታዋቂ ሆቴሎች የሠራና ብዙ ልምድ ያለውን ፈረንሳዊ የምግብ አዘጋጅ (ሼፍ) መቅጠሩንና በፓሪስ ሂልተን በኃላፊነት ትሠራ የነበረችውን ፈረንሳዊት በኦፕሬሽን ማናጀርነት ማምጣቱን አስታውቋል። እንዲሁም ሠራተኞቹ እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ፣ ዐረብኛ፣ ፈረንሳይኛና ኪስዋሂሊ አቀላጥፈው የሚናገሩ ስለሆነ፣ ከእንግዶች ጋር የመግባባት ችግር እንደማይኖርና ከፍተኛ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቋል፡፡
የሆቴሉ ግንባታ 95 ከመቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ጥቂት የሚቀር ሥራ ስላለው ወጪው በትክክል ያለመሰላቱን ባለ ሀብቱ ጠቅሶ፣ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 200 ሚሊዮን ያህል ብር እንደሚፈጅና ለ143 ዜጐች የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ በአጠቃላይ ሥራው ሲጠናቀቅም የሠራተኞቹ ቁጥር 250 እንደሚደርስ ተናግሯል - አቶ ወንድወሰን፡፡
ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቃቸው የእንግዶቻቸው ደኅንነት በመሆኑ፣ 67 የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎችና እሳት ቢነሳ ጪስ ጠቋሚ መሳሪያዎች መተከላቸውን፣ በሪሞት መቆጣጠሪያ የሚታዘዙት አምፑሎች 12 ዓይነት ቀለም እንደሚፈነጥቁ፣ … ተገልጿል፡፡ ከጃፓን የተገዙት የመታጠቢያ ክፍል ዕቃዎች ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ሲሆን የ30 ዓመት ዋስትና የተረጋገጠላቸው መሆኑም ተነግሯል፡፡
የቤላ ቪው ሆቴል ግንባታ ስድስት ዓመት ያህል እንደፈጀ የጠቀሰው አቶ ወንድወሰን፣ ቦታው ዳገት ላይ በመሆኑ በተፈጠረው አስቸጋሪነት፣ የሚያምርና የሚያኮራ ነገር ለመሥራት በመፈለጋቸውና አንድ አገልግሎት ሰጪ መ/ቤት በፈፀመባቸው በደል፣ ግንባታው ሊዘገይ መቻሉን ገልጿል። የተፈፀመባቸው በደል ምን እንደሆነ ተጠይቆ ሲመልስ፣ “ጥሩ መ/ቤቶች የመኖራቸውን ያህል በደል የፈፀመብንም አለ፡፡ ሙስና ገንዘብ መስጠትና መቀበል ብቻ ሳይሆን የመልካም አስተዳደር ጉድለትም ሙስና ነው፡፡ ይህን ኢንቨስተሮችን የሚያባርር በደል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ማወቅ አለበት፡፡ አራት ኪሎ የሚገኘው የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ጽ/ቤት ከፍተኛ በደል አድርሶብናል፡፡ ያልገባንበት ባለሥልጣንና ኃላፊ ቢሮ የለም፡፡ ሊያነጋግሩን እንኳ ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ይኼ ሆቴል ሥራው ያለቀው ከአምስት ወር በፊት ነው፡፡ መብራት ስለሌለን፣ የተገጠሙትን ዘመናዊ መሳሪያዎች መሞከር አልቻልንም፡፡ እንቢ ብለውን ቆይተው “እንግዲያውስ አገሪቷን ጥለን እንወጣለን” ስንላቸው በስንት መከራ ባለፈው ሳምንት አስገቡልን፡፡ የዚያኑ ያህል ጥሩ መ/ቤቶችም ስላሉ መመስገን አለባቸው። ቴሌና የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን እራሳቸው አስገብተውና ፈትሸው ነው ያስረከቡን፡፡ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የመብራት ኃይል በደል በእኛ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎችንም እያስለቀሰ ነው፡፡ አንተ ዕድለኛ ነህ፤ እኛ ከ8 ወር በላይ ጠብቀን አልሆነልንም’ ያሉኝ አሉ” በማለት ምሬቱን ገልጿል፡፡
ለበርካታ ዓመታት ስዊስ የኖረው አቶ ወንድወሰን አትሌት የነበረ ሲሆን፣በአሁኑ ወቅት የባለቤቱ የማርያምና የባህሬን ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን አሠልጣኝ ነው፡፡  

እ.ኤ.አ ኦክቶቨር 17/20013 በኢትዮጵያ ደግሞ ጥቅምት 7/2006 ዓ/ም ጾታን መሰረት ባደረገ ጥቃት ምክንያት ለሚደርሱ የአካል፣ የስነልቡና ፣የህግና የጤና ችግሮች በአገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ማእከል ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል አንድ ወጥ መመሪያ በማስ ፈለጉ በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ ውይይት ተደርጎአል፡፡ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስ..ር አስተባ ባሪነት ከህግ፣ ከፖሊስ ከስነልቡና ፣ ከሴቶች ወጣቶች እና ህጻናት ሚኒስ..ር የተውጣጡ ሙያ ተኞች በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሮጀክት ቢሮ ስብሰባውን ሲያደርጉ የማህበሩ አባላት እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች አስፈላጊውን ገለጻ አድርገዋል፡፡ ይህንን ረቂቅ በማዘጋጀት ረገድም በኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሮጀክቱን ሲመሩ የቆዩ የማህበር አባላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ስብሰባውን እንዲከፍቱ የተጋበዙት የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት ነበሩ፡፡ ዶ/ር ይርጉ እንደገለጹት...
“...የስብሰባው አላማ የጾታዊ ጥቃት የደረሰበት ሰው ወደ ሕክምና በሚመጣበት ጊዜ ሊደረግለት የሚገባው አገልግሎት በምን መልክ መሆን አለበት የሚለውን ለመፈተሸ ነው፡፡ የጾታዊ ጥቃትን በሚመለከት ለሚሰጠው ስልጠና ካሪኩለም ተዘጋጅቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ስራ ላይ ውሎአል፡፡ ነገር ግን የስራ ሂደቱን በሚመለከት ወጥነት የሚጎድለው አካሄድ ስለአለ አሁን የሚደረገው ጥረት ይህንን ለማስተካከል ነው፡፡ በአብዛኛው ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ስለሆኑ አንዲት ሴት ይህ ችግር ሲገጥማት ወደህክምና መስጫ ተቋም ወይንም ወደ ህግ ተቋም እንዲሁም ወደስነልቡና አገልግሎት ልትሄድ ትችላለች፡፡ ይህም አንዲት ጥቃት የደረሰባት ሴት በመጀመሪያ ልታገኛቸው የምትፈልጋቸው ተቋማት እንደሆኑ እርግጥ ነው። ነገር ግን መንገዱን ከጀመሩት በሁዋላ የሚገጥማቸው ችግር ቀላል የማይባል ነው፡፡ ...ለምሳሌ ወደ ጤና ተቋም ብትሄድ በመጀመሪያ ከፖሊስ ወረቀት አምጪ ልትባል ትችላለች። ወደህግ ቦታ ስትቀርብ ደግሞ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የህክምና ሁኔታዎች ቸል ሊባሉ የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራል። ስለዚህም የስራ ሂደቱ ወጥ ቢሆን እንዲሁም የሚሰሩት ስራዎች የህክምናው ለህግ ፣ የህጉ ለሕክምናው ግልጽ ቢሆኑ እንዲሁም የማህበራዊእና የስነልቡና ስራ የሚሰሩት ባለሙያ ዎች አሰራራቸው ግልጽ ቢሆን የሚሰጠው አገልግሎት የተሳካ ይሆናል፡፡ አገልግሎቱም በሁለት መልክ መፍትሔ የሚሰጥ ይሆናል የሚል እምነት ይኖራል፡፡
1. ጥቃትን መከላከል የሚያስችል ፣
2. ጥቃት ከደረሰም አስፈላጊውን እርዳት ሁሉ...ሕክምና...ሕግ...የማህበራዊና ስነልቡና አገልግሎት ድጋፍ መስጠት የሚቻልበት የስራ ሂደት ይፈጠራል .....ብለዋል፡፡
በረቂቅ ዶክመንቱ ላይ እንደሚነበበው...ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ሲባል ወንድንና ሴትን ሳይለይ በሁለቱም ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የሚመለከት ቢሆንም በተለምዶ የሚታየው ግን በተለይ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በዚህ ዘርፍ ተጎጂ ሲሆኑ ነው፡፡ ለዚህም እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው በወንዶችና ሴቶች መካከል ያለው ኃይል ወይንም አቅም ተመጣጣኝ አለመሆኑ ነው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አገላለጽ መሰረት በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ጾታን መሰረት ያደረገ እና በአካል እንዲሁም ስነአእምሮ ላይ ጉዳት ከማድረሱም በተጨማሪ ተያይዞ ለሚመጣ የስነልቡና ጉዳት የሚዳርግ ነው፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት አለምአቀፋዊ ሲሆን መሰረቱ እሩቅ የሆነ እንዲሁም ዘዴ የተሞላበት የኃይል አለመጣጣም የሚታይበት ከመሆኑም ባሻገር በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን የአካል ተፈጥሮአዊ ልዩነት በግልጽ የሚታይበት ነው። በዚህም ምክንያት ጀንደር በሚለው የማህበራዊ ስርአት አወቃቀር ለሴቶች እና ለወንዶች ሲሰጥ የኖረውን ደረጃ እና የአኑዋኑዋር ዘይቤ ምን ያህል ሴቶች ላይ ጫና ያደርስ እንደነበር መገለጫው ነው፡፡ ለዚህ ምስክሩም ብዙውን ጊዜ ወንዶች በሴቶች ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት በህብረተሰቡ ዘንድ እንደ ጥፋት ሳይቆጠሩ እንዲያውም የሚወሰደው የህግ እርምጃ አነጋጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ በብዙ ሀገሮች የሚስተዋል በመሆኑ ነው፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የት እና እንዴት ወይንም በማን ተብሎ ሊከፋፈል የማይችል በአጠቃላይም የትም ቦታ ፣በማንኛውም ሰው ተብሎ ሊገለጽ እንደሚችል ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት በቤት ውስጥ፣ በመኖሪያ አካባቢ፣በትምህርት ቤት ፣በስራ ቦታ ...ወዘተ ሊደርስ እንደሚችል የተለያዩ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃቶች በቤተሰብ፣ በጉዋደኛ፣ በስራ ባልደረባ፣ በማያውቁት ሰው ...ወዘተ ሊፈጸሙ የሚችሉ ጉዳቶች ናቸው፡፡
በጾታ ጥቃት ምክንያት ጉዳት መድረስ ማለት የሰብአዊ መብትን እንደመጋፋት የሚቆጠር ነው፡፡ ለዚህም እማኝ የሚሆኑት የተለያዩ አለምአቀፋዊ መድረኮች ናቸው፡፡ ለምሳሌም...
(CEDAW) 1979, World conference on human rights ,Viena,1993, International conference on population and Development (ICPD),Cairo,1994, UN fourth conference of women ,Beijing ,1995,Declatation of the General Assembly of the united nations on the elimination of Violence against Women,,. Beijing platform of Action, Millennium Development goals(MDGs)…. ወዘተ
ከላይ ለምሳሌነት የተጠቀሱት አለምአቀፍ ስብሰባዎችና ሌሎችም መድረኮች በተስማሙበት መሰረትም በጾታ ጥቃት ያደረሰ ሰው አስፈላጊውን የህግ ቅጣት እንዲያገኝ ሐገሮች የተስማሙበት ሲሆን ለተጎጂዎችም የአካል ጤንነት እንዲሁም የህሊና ነጻነት የሚያስገኝ ነው፡፡
በወሲባዊ ጥቃት ምክንያት የሚደርሰው የጤና ችግር የህብረተሰብ የጤና ችግር ተደርጎ የሚወሰድበት መንገድም አለ። አንዲት ሴት በደረሰባት ወሲባዊ ጥቃት ምክንያት ከሚደር ሱት የጤና እውክታዎች መካከል ...የአካል ጉዳት...ከባድ የእራስ ሕመም...በቋሚነት ሊገጥም የሚችል የጀርባ ሕመም... የስነልቡና መቃወስ ...እንደ ድብርት ...ፍርሀት ...እንቅልፍ ማጣት ...መርሳት... በራስ የመተማመን ብቃትን ማጣት የመሳሰሉ ችግሮች ሊገጥሙዋት ይችላሉ፡፡ በዚህም ምክን ያት አብዛኛውን ጊዜ በእራሳቸው ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚሞክሩ ሴቶች በርካታ ናቸው፡፡ የእና ቶችን ሞት ከሚያባብሱ መካከል የሚመደብ ሲሆን ለኤችአይቪ ኤድስ ተጋላጭ የሚሆኑትም ቀላል የሚባሉ ኤደሉም፡፡
ጾታን መሰረት ያደረገ ወሲባዊ ጥቃት የኢኮኖሚም ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ተጋላጭ የሆኑ ግለሰቦች በሚደርስባቸው የጤና መጉዋደል ምክንያት የእራሳቸው እንዲሁም የቤተሰባቸው ገቢ ከመቃወሱ በተጨማሪ ለአገልግሎቱ የሚውለው ወጪ ብዙ ነው፡፡ አንድ ጥናት እንደሚያ መለክተው በባንግላዴሽ በ2010/ በአጠቃላይ የቤት ውስጥ ጥቃት በገንዘብ ሲሰላ 1.8/ቢሊዮን ዶላር ያህል ነበር፡፡ በ1996 እ.ኤ.አ በቺሌ በተደረገው ጥናት ሴቶች በሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃት ምክንያት ሊያገኙት የሚገባቸውን ወደ 1.56/ ቢሊዮን ዶላር አጥተዋል፡፡ በዚሁ መልክ የተለያዩ ሐገሮችን እውነታ ጥናቶች የሚያሳዩ ቢሆንም ወደሀገራችን መለስ ስንል ግን ዝርዝር በሆነ መልክ መረጃውን ማግኘት የሚያስችል ጥናት አልተደረገም፡፡ ቢሆንም ግን ከተለያዩ መረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው በገጠርም ይሁን በከተሞች ችግሩ በሰፋ መልኩ የሚስተዋል መሆኑን ነው። በወሲባዊ ጥቃት ብቻም ሳይሆን በአጠቃላይ በቤት ውስጥ ጥቃት ምን ያህል ሴቶች ተጎጂ ሆነዋል የሚለውን ለመለካት ባይቻልም እንኩዋን በ2011 /በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው..ሃመ እንደተመለከተው ብዙ ሴቶች መብታቸውን እንደማያውቁና ወንዶችም ሴቶ ችን መጉዳት እንደጥፋት የማይቆጥሩት መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌም በዳሰሳ ጥናቱ ከተካተቱት ተሳታፊ ሴቶች 68 ኀ ወንዶች ቢመቷቸው ምንም ነውር እንደሌለበት የገለጹ ሲሆን 45 ኀ የሚሆኑት ወንዶች ደግሞ ሴቶች በወንድ መመታታቸው አግባብነት ያለው አድርገው እንደሚቀበሉት ተናግረዋል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት ከልማት ጋር የሚያያዝ ጉዳይም ነው፡፡ የምእተ አመቱን የልማት ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ ነጥቦችን መከወን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመቀነስ እንደሚረዳ እሙን ነው፡፡ አገራት በዚህ ዘርፍ በጥንካሬ መስራት እንደሚጠ በቅባቸው የአለም የጤና ድርጅት አስምሮበታል ..ሳሳቈስቋቋሽቃሸ ባሽቄቁስቃሰስ ሮሸሮሽቃቋ.. ብቄቂስቃ ሮቃሳ ሮሰሻሽስባሽቃሸ ..ሻስ ቂሽቁቁስቃቃሽበቂ ሳስባስቁቄቅቂስቃ.. ሀቄሮቁቋ ፡ሠሃሑ 2005...
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት የጾታን ጥቃት በሚመለከት በማህበሩ ሲሰራ የቆየውን እና ወደፊት ምን ለማድረግ እንደሚገባ ሲገልጹ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

.....ቀደም ባለው ጊዜ ይህንን ጥቃት በሚመለከት ደረጃውን ያልጠበቀ ሕክምና እና ደረጃውን ያልጠበቀ የህክምና ማስረጃ የሚሰጥበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2001 -2002/ ድረስ ባለው ጊዜ የተወሰኑ ሞዴል ክሊኒኮችን በመስራት እና ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በአንድ ተቋም ውስጥ የተሟላ አገልግሎት የሚያገኙበትን እና በተቻለ መጠንም በቂ የሆነ ሕጋዊ ማስረጃ የሚያገኙበትን ሁኔታ ሲያመቻች ቆይቶአል። ከዚያም በሁዋላ ይህንን በአዲስ አበባ ብቻ ሲሰጥ የቆየውን አገልግሎት ወደሌሎች መስተዳድሮችም በ ማስፋፋት በአዳማና በአዋሳ ሞዴል ክሊኒኮቹን በማመቻቸት ስራዎች እየተሰሩ ቆይተ ዋል፡፡ለወደፊቱም ያለው እቅድ አሁን ያሉትን ሞዴል ክሊኒኮች ከሁለት ወደሰባት ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ማእከላቱ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ናቸው፡፡ የዚህም ምክንያቱ በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት ከተቻለ ከዚያ የሚወጡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የቅድመ ምረቃ እና የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ወደስራ በሚሰማሩበት ወቅት አገልግሎቱን በተቻለ ፍጥነትና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ሊያስፋፉ ይችላሉ የሚል እምነት ስለአለ ነው..... ብለዋል ፡፡
ይቀጥላል

Published in ላንተና ላንቺ

             የእንግሊዛዊው ፀሐፌ ተውኔት ዊሊያም ሼክስፒር ድንቅ የተውኔት ስራ የሆነው “ኦቴሎ” በትግርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በመፅሃፍ ወጣ፡፡ ተውኔቱን ወደ ትግርኛ ለመመለስ አንድ ዓመት እንደፈጀበት ያስታወሰው አንጋፋው ደራሲና መምህር ኃይለመለኮት መዋዕል፤ ለዚህ ሥራው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የተረጎመውንና በርካታ የተውኔቱን የእንግሊዝኛ ቅጂዎች እንደተጠቀመ ገልጿል፡፡ ተውኔቱ ለመድረክ ይበቃ እንደሆነ የተጠየቀው ተርጓሚው፤ መፅሃፉን ያሳተመው በብድር እንደሆነና ለመድረክ ዝግጅት አቅም እንደሌለው ጠቅሶ፤ ስራውን ያዩ ግለሰቦች ግን ወደ መድረክ ሊለውጡት እንደሆነ ተናግሯል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር ዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ ገዛኸኝ ፀጋውና ሌሎች ተባባሪዎች ባደረጉት ጥረትም የትግርኛ ቋንቋ በሚሰጥባቸው ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች መፅሃፉ ለማስተማርያነት ሊሰራጭ እንደሆነ አክሎ ገልጿል፡፡
120 ገፆች ያሉት “ኦቴሎ” የተውኔት መፅሃፍ፤ በአይናለም፣ በሜጋ እና በዩንቨርሳል መፃህፍት መደብሮች በ30 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡ ኃይለመለኮት ተውኔቱን በ1964 ዓ.ም የተረጎመው ሲሆን በአብዮቱ ጊዜ መሰል መፅሃፍት ተሰብስበው ሲቃጠሉ በወንድሙ አማካኝነት ቆፍሮ በመቅበር፣ ከ42 ዓመታት በኋላ አሻሽሎ ለንባብ እንዳበቃው ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፤ በዶክተር ዮናስ አድማሱ አርታዒነት አምና ለንባብ ያበቃው “የዮፍታሄ ህይወትና ስራ” ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት በብሄራዊ ቤተመጻሕፍት ውይይት እንደሚደረግበት ሚዩዚክ ሜይዴይ አስታወቀ።
ውይይቱን የሚመሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር መምህር የሆኑት አቶ አሰፋ ወርቁ ናቸው፡፡

ደራሲና ሀያሲ ፍቃዱ ልመንህ ያዘጋጀውና ስለ ፊልም ጥበብ የሚያትተው “የአቡጄዲ ግርግር” መጽሐፍ ዛሬ ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ በጣይቱ ሆቴል “ጃዝ አምባ” እንደሚመረቅ ዮዳሔ ሕትመትና ፊልም ሥራ አስታወቀ፡፡ በዕለቱ አንጋፋው የፊልም ባለሙያ ብርሃኑ ሽብሩ በመጽሐፉ ላይ ዳሰሳ የሚያቀርብ ሲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምሕር ጳውሎስ አዕምሮ “የኢትዮጵያ ፊልም የወደፊት ዕጣ ፈንታ” በሚል ርእስ የመወያያ ጽሑፍ ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ “የአቡጄዲ ግርግር” በሃያ አንድ የኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ የተሰሩ ሂሶችን አካትቷል፡፡

አርባ ሠዓሊዎች ትናንት ሥራዎቻቸውን በሰኔሬድ አቀረቡ
የሠዓሊ ብሩክ የሺጥላ ሥራዎች የሚቀርቡበት “የኔታ” የተሰኘ የስዕል ኤግዚቢሽን ከትላንት በስቲያ በላፍቶ አርት ጋለሪ ተከፈተ፡፡ በኤግዚቢሽኑ የቀረቡት ሥዕሎች አዳዲስ ሲሆኑ ኤግዚቢሽኑ ለሁለት ሣምንታት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል አርባ ሠዐሊዎች ትናንት ከሰአት በኋላ በሰነሬድ ሬስቶራንት የስዕል ኤግዚቢሽን አቅርበዋል፡፡ ሠዓሊዎቹ የሥዕል ኤግዚቢሽኑን ከማቅረባቸው በፊት ስራዎቻቸውን ለአድናቂዎቻቸው እንዳሳዩ ታውቋል፡፡

በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ በሚያቀርባቸው ወጎችና መጣጥፎች የሚታወቀው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያዘጋጀው “አራቱ ኃያላን” አዲስ መጽሐፍ በመጪው ሳምንት እሁድ 4 ሰዓት ላይ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንደሚመረቅ “አግዮስ ሕትመትና ጠቅላላ ንግድ” አስታወቀ፡፡ በምረቃው ዕለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ፣ ዶ/ር ውዱ ጣፈጠ እና ዶክተር አምሳሉ ተፈራ በመጽሐፉ ላይ አስተያየት እንደሚሰጡ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች ዝርዝር የያዘ የተፈጥሮ ፓርኮች ማውጫ ታትሞ መውጣቱን “ሀገሬ ኮሙኒኬሽን” አስታወቀ፡፡ ከትናንት በስቲያ በነፃ መሠራጨት የጀመረው ቅጽ ፩ ማውጫ፣ 118 ገፆች ያሉት ሲሆን 59 ወንዞች፣ 40 ተራራዎች፣ 26 ሐይቆች፣ 24 ፓርኮች፣ 12 ዋሻዎች እና ሌሎችም በርካታ መረጃዎችን አካትቷል፡፡ “ቱባ” የተሰኘውን በየሁለት ወሩ የሚወጣ የቱሪዝምና ባሕል መጽሔት እያሳተመ የሚያሰራጨው “ሀገሬ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን”፤ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የቱሪዝም ማውጫ ሲያዘጋጅ የአሁኑ ሁለተኛው ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት የሰሜን ሸዋ ዞንን መስሕቦች የሚያስተዋውቅ ማውጫ ማዘጋጀቱ ይታወሳል። ድርጅቱ የጎንደር መስሕቦች የሚተዋወቁበት ማውጫ በቅርቡ ለማስመረቅም በዝግጅት ላይ እንደሆነ ገልጿል። የ“ሐገሬ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን” ሥራ አስኪያጅና የተፈጥሮ መስህብ ዳይሬክተሪው ዋና አዘጋጅ አቶ ሄኖክ ስዩም ስለማውጫው ሲናገሩ፤ “የሀገራችን የተፈጥሮ ሀብቶች ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ልማት እንዲውሉና ሀገራችንን እንድንጎበኝ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው” ብለዋል፡፡

ከመቶ ሃምሳ አመታት በፊት፣ በጉራጌ የሴቶች መብት ተሟጋች እንደነበረች በሚነገርላት የቃቄ ወርድዎት ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን በጥናት ላይ የተመሰረተ “የቃቄ ወርድዎት” የተሰኘ ትያትር በቅርቡ ለተመልካች እንደሚያቀርብ ብሔራዊ ትያትር ገለፀ፡፡
ትያትር ቤቱ ይሄን ትያትር ለማቅረብ ባለፈው ማክሰኞ ከጉራጌ ዞን አስተዳደር፣ ከጉራጌ ልማት ማሕበር እና ከቤተ ጉራጌ ባሕል ማዕከል ጋር የ1ሚ.259ሺ ብር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርአቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ ትያትር ቤት ዳይሬክተር ጀነራል አርቲስት ተስፋዬ ሽመልስ፤ ትያትሩ ከፆታ ጋር የተያያዙ የግንዛቤ ችግሮችን ለማስወግድ እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡ “ትያትር ቤቱ ትያትሮች ከኢንተርኔት እየታጨዱ የሚቀርብበት አይደለም” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች ቦታ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው፤ የቃቄ ወርድዎት “ለወንዶች ብዙ ሚስት ከተፈቀደ ለሴቶችም ብዙ ባል መፈቀድ አለበት” ማለቷን በመጥቀስ ለሴቶች መብት መከበር ያደረገችውን አስተዋፅኦ አብራርተዋል። “የቃቄ ወርድዎት” የተሰኘውን ትያትር የደረሰው ፀሃፌተውኔት ጫንያለው ወልደጊዮርጊስ ሲሆን “አዳብና” የተባለውን ትያትር ለመድረክ ያበቃው ዳግማዊ ፈይሳ እንደሚያዘጋጀውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ግማሽ-መንገድ መሄድ ይቅር እንዝለቅ እስከጐሉ ጫፍ
ድጋፍ የለም በግማሽ-አፍ’ ከልባችን እንደግፍ!
የወረት ነው የሚመስል-ካሸናፊ ጋራ እፍ-እፍ
አኪሩ ሲዞር ማቀርቀር-ተሸናፊን ረግጦ ማለፍ!
መቼ በኳስ ብቻ ሆነ - ታይቷል በሌላም ምዕራፍ፡፡
ቋሚ እንሁን እንጽና’እንጂ ከእሳት ወደ በረዶ
መወንጨፍ ከጽንፍ ወደ ጽንፍ
ክñ አመል ነው ዥዋዥዌ-ዛሬ ጓዳ@ነገ ደጃፍ”
ስናገባ ብቻ ዘራፍ!
ስንሸነፍ ጉልበት ማቀፍ!
ሲሞቅ እንደ እንፋሎት መትነን@
ሲበርድ እንደግዑዝ ነገር’ፍፁም ዲዳ በድን መሆን
እሪ ስንል ጐል አግብተን’ያመት-ባል ገበያ መስለን@
በለስ ነስቶን ድል ባይቀናን
ሬሳ የወጣው ቤት መሆን@
ኧረ ጐበዝ! ቋሚ እንሁን !
ገብቶ መፋለም ቢያቅተን
መደገፍ እንዴት ይጥፋብን?!
ከፊልሙ እንዳልተዋደደ
ከግብሩ እንዳልተዋሃደ
ከትወናው ጋራ ሠምሮ’ወጥ ሆኖ አብሮ እንዳልሄደ
ከቦክስ ኋላ እንደሚመጣ’የቀሽም ፊልም አጃቢ ድምጽ
ከድርሰቱ እንደተፋታ’እንዳላማረ ኮሾ አንቀጽ
ሙሉ ጨዋታ መደገፍ’መጮሁ እንዴት ያቅተን?
በቴፕ አፍ የተፈጠረ’የዲጄ ነው እንዴ ድምፃችን?
ባገርም ጉዳይ ይሄው ነው፡-
ቅጥ-አንጣ በድላችን
ሲበልጡን ቆፈን አይያዘን-
መቼም መቼም የትም ቢሆን
ሙሉ ጊዜ ቋሚ እንሁን! እናግዝ ልጆቻችንን!
መቼም ኢትዮጵያዊነትን’የውጪ ባዕድ አልሰጠን
እኛው ውስጥ የበቀለ እንጂ’ “የዲጄ” አይደለም ድምፃችን
ብንሸነፍም እኛው’ብናሸንፍም እኛው ነን!
በወረት አንለዋወጥ’እንደግፍ ከልባችን!
እናግዝ አገራችንን!!
(ለኢትዮ-ናይጄሪያ የኳስ ፍልሚያና ለኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች) ኀዳር 2 ቀን 2006 ዓ.ም

Published in የግጥም ጥግ