ረቡዕ ምሽት በጩቤ የተወጋው የ16 አመቱ ዳዊት መስፍን፤ በመኖሪያ ቤቱ ደጃፍ የሞተ ሲሆን፣ በእግር ኳስ ሰበብ በተከሰተ ፀብ ግድያውን ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሶስት ታዳጊዎች በፖሊስ ተይዘዋል፡፡ ዳዊት እና ተጠርጣሪዎች ከአንድ አመት በፊት በእግር ኳስ ክበብ ተጣልተው እንደነበር የሚናገሩት የሟች እናት፣ ብዙ ጊዜ ይዝቱበት ነበር ብለዋል፡፡

በዛቻ ብቻ ሳይመለሱ፣ ታላቅ ወንድሙን በጩቤ ወግተው ለመግደል ሞክረው ነበር የሚሉት እኚሁ እናት፤ የግድያ ሙከራውን ለፖሊስ አመልክተን ለጊዜው ቢታሰሩም ወዲያው ተለቀቁ በማለት ያስታውሳሉ፡፡ ረቡዕ ማታ ከሁለት ሰዓት በኋላ ስልክ ተደውሎለት ከቤት የወጣው ዳዊት፤ ሳይመለስ እንደቀረ እናቱ ገልፀው፣ ወንድሙና ጓደኛው በር ላይ ሞቶ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡

የ10ኛ ክፍል የምስራቅ ጐህ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረው ዳዊት፤ ፀብ የማይወድ ልጅ እንደነበር የሚናገሩት አባቱ አቶ መስፍን አስራት፤ ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ በፊት ቤተክርስቲያን አግኝተውት ሊጣሉት ፈልገው ነበር ብለዋል፡፡ ሲተናኮሉት ቆይተው ረቡዕ ምሽት ገደሉት፤ በዚያው ምሽት ተይዘው ጩቤውን ለፖሊስ አሳይተዋል ብለዋል አቶ መስፍን፡፡ ፖሊስ በበኩሉ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡

Published in ዜና

ሠሞኑን በሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ እየደረሠ ያለው ግፍና ስቃይ እንዳሳዘናቸው የገለፁ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ የሣውዲ አረቢያ መንግስት እና የኢትዮጵያ መንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ተናገሩ፡፡ የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ ሣውዲ አረቢያ የራሷንም ዜጐች መብት የማታከብር ሃገር መሆኗን ገልፀው፣ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመው አሠቃቂ ስራ ግን በ21ኛው ክ/ዘመን የማይጠበቅ ግፍ ነው ብለዋል። በተለይ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ድርጊት አስነዋሪ ነው በማለት መወገዝ እንዳለበት የተናገሩት ዶ/ር መራራ፤ ዋናው ተጠያቂ የሳውዲ መንግስት ነው ብለዋል፡፡

“በሌላ በኩል ኢህአዴግ ሃገሪቱን የስደት ሃገር አድርጓል” ያሉት ዶ/ር መረራ፤ በሜድትራኒያን፣ በየመንና በደቡብ አፍሪካ መስመሮች የሚሰደዱ ዜጐቻችን የአውሬ ሲሣይ እየሆኑ ነው፤ በሃገር ውስጥም በውጭም የዜጐቹን መብት ማስከበር ያልቻለው የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ መሆን አለበት” ብለዋል፡፡

በሣውዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ በትኩረት እየተከታተሉ መሆናቸውን የሚገልፁት የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በዜጐቻችን ላይ የተፈፀመውን ድርጊት ለመከላከልና ለማስቆም አለመቻሉ መንግስት አልባ መሆናችንን የሚያሣይ ነው ብለዋል፡፡ አቶ አበባው እንደሚሉት፤ የሌላ ሃገር መንግስት ቢሆን ኖሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን እዚያ ሃገር ድረስ ልኮ ሄዶ የዜጐቹን መብት ያስከብር ነበር ብለዋል - አቶ አበባው፡፡ እዚህ ሃገር የውጭ ዜጐች ከቀን ሠራተኛነት ጀምሮ በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ መብታቸው ተከብሮላቸው ይኖራሉ ያሉት አቶ አበባው፤ “የኛ ዜጐች በሳውዲ ከሰውነት በታች ተዋርደው ግፍ የሚደርስባቸው ለዜጐች የሚቆረቆር መንግስት ስለሌለ ነው” ብለዋል፡፡ ለዜጐቻችን ሠቆቃ የመጀመሪያ ደረጃ ተጠያቂው የኢትዮጵያ መንግስት ነው በማለት የሚናገሩት አቶ አበባው፤ ዜጐች በሃገራቸው የስራ እድል የሚያገኙበትን አማራጭ ማስፋት የመንግስት ሃላፊነት ቢሆንም፤ በተቃራኒው በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ብሎኬት የሚሠሩት፣ ሹፌር የሚሆኑት፣ አሣማ የሚያረቡትና የመሣሠሉትን ስራዎች የሚሠሩት የውጭ ሃገር ዜጐች ሆነዋል” ብለዋል አቶ አበባው።

የሣውዲ አረቢያ መንግስት “ከሃገሬ ውጡልኝ” ቢል እንኳ፤ የስደተኞችን ሰብአዊ ክብር በጠበቀ መልኩ ማስፈፀም ነበረበት ያሉት አቶ አበባው፤ “ነገር ግን ኢትዮጵያውያኑ በፖሊስ እየተገደሉና እንደ አውሬ እየተሣደዱ ነውና በዚህም የሣውዲ መንግስት ተጠያቂ ይሆናል” ብለዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ በተለያዩ የማህበራዊ ድረ ገፆችና መገናኛ ብዙሃን ላይ የሠላማዊ ሠልፍ ጥሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ መግለጫዎችን ሲሠጥ የነበረው የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፤ የሣውዲ አረቢያ መንግስት ህገወጥ የሚላቸውን ስደተኞች በህገ ወጥ መንገድ ማሠቃየቱ በምንም መዘዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው ገልፀው፤ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ደካማነት የሚያረጋግጥና የኢትዮጵያንም ህዝብ የሚንቅ ድርጊት ነው ብለዋል።

የአገራችን ባለስልጣናት ጉዳዩን የተመለከቱበት መንገድ አሣዝኖኛል፤ አሣፍሮኛልም ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ “ጥንታዊ ታሪክና ክብር ካለው ሃገር መሪዎች የሚጠበቅ አይደለም” ብለዋል፡፡ በየአመቱ አንድ ሚሊዮን ስራ አጥ እየተፈጠረ መሆኑን የሚናገሩት ኢ/ር ይልቃል፤ ወጣቱን ለስራ ፈጣሪነት የሚጋብዝ ነገር አለመኖሩ አንድ የስደት መንስኤ ነው ብለዋል፡፡ “የተማረና አቅሙ የፈቀደ በቦሌ ይሄዳል፤ ያልተማረው ደግሞ ውሃ ይብላኝ እያለ በረሃ እያቋረጠ ይሄዳል” የሚሉት ኢ/ር ይልቃል፤ “አገር እያደገች ዜጐች ስደትን ይመርጣሉ የሚለው የባለስልጣናት አባባል ውሸት ነው” ይላሉ፡፡ የሣውዲ አረቢያ መንግስት በዜጐች ላይ የፈፀመው አሠቃቂ ድርጊት ሳያንስ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና የመንግስት ሚዲያ ለጉዳዩ የሠጡት አናሣ ትኩረት አሳዝኖኛል ብለዋል - የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር፡፡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጐቻችን ሲሰቃዩና የሰው ህይወት ሲጠፋ፣ መንግስት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አልሰጠም የሚሉት ኢ/ር ይልቃል፤ የኢትዮጵያ እና የሣውዲ አረቢያ መንግስት በእኩል ደረጃ ተጠያቂ ናቸው ብለዋል፡፡

የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ጉዳዩን በአፅንኦት እየተከታተለው መሆኑን ገልፀው፤ በሳውዲ የተፈፀመው ተግባር በእጅጉ የሚያሣፍር እና የሚያሣዝን ነው ብለዋል። ማንኛውም ሃገር የራሱን ህግና መመሪያ ሊያወጣ ይችላል ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ ይሁን እንጂ “ፍቃድ አላሣደሡም” በሚል ሰበብ ዜጐቻችን የሠው ልጅን ክብር በሚያዋርድ ሁኔታ ለስቃይ መዳረጋቸው ብሄራዊ ሃፍረት ነው ብለዋል። ድርጊቱን በፈፀሙት አካላት ላይ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን ዶ/ር ነጋሶ ጠቅሰው፤ የሣውዲ አረቢያ መንግስትና የፖሊስ ሃይሉ በህግ ሊጠየቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

“አሁን ግን በዜጐቻችን ላይ እየተፈፀመ ባለው ድርጊት የአገራችን ሉአላዊነት ተነክቷል፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን የማስጠበቅ ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም” ብለዋል ዶ/ር ነጋሶ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጠበቅ ያለ አቋም መውሠድ እንዳለበትና ዜጐች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ በአስቸኳይ መፍትሔ መስጠት እንዳለበትም አሣስበዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ስራ አጥነትና የመሣሠሉት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የሃገሪቱን ዜጐች ለስደት እየዳረገ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ነጋሶ፤ መንግስት ድክመቱን እንዲያሻሽል ሁሉም ዜጋ ግፊት ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

Published in ዜና

ዩኒቨርስቲዎች የውሃ እጥረት ለማቃለል እየጣርን ነው ብለዋል

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በውሃ እጦት ረቡዕ እለት ሰልፍ ከወጡ በኋላ በርካታ ተማሪዎች የታሰሩ ሲሆን፤ ለሦስት ሳምንት ውሃ መቋረጡን በመቃወም የተሰበሰቡ የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የግቢው ጥበቃ እንደበተናቸው ተገለፀ፡፡ በአቃቂ የሚገኘው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በውሀ እጦት መቸገራቸውንና ሰሚ ማጣታቸውን ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲዎቹ አስተዳደሮች በበኩላቸው፤ ውሃ ጨርሶ ጠፍቷል መባሉ የተጋነነ አባባል ነው በማለት፣ የውሃ እጥረት ለማቃለል እየጣሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በውሃ እጦት የተነሳ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳካሄዱ የተናገሩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ረቡዕ ማታ የከተማዋ ፖሊስ የዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በመግባት በርካታ ተማሪዎችን እንዳሰረ ገልፀዋል፡፡ በማግስቱ የተወሰኑ ተማሪዎች ከእስር መለቀቃቸውንና ግቢው መረጋጋቱም ተነግሯል፡፡

ውሃ ካጣን ሦስት ሳምንት ሆኖናል የሚሉት የአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ የዩኒቨርስቲ አስተዳደር መፍትሔ ሊሰጠን አልሞከረም ብለዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች ተሰባስበው ሁለት ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲሞክሩ በግቢው ፖሊሶች እንደተበተኑ ተማሪዎቹ ጠቅሰው፤ አንድ ጄሪካን ውሃ ለመቅዳት ከሶስት ሰዓት በላይ ለወረፋ እንቆማለን ብለዋል፡፡ በሁለት ቀን አንዴ ውሃ ታገኛላችሁ ተብለን በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ፕሮግራም ቢለጠፍም፤ በተባለው ቀን ውሃ አግኝተን አናውቅም ያሉት ተማሪዎቹ፤ ለንጽህና ቀርቶ የመጠጥ ውሃ የምናገኘው በግዢ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርስቲው የአለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ታጉ ዘርጋው፤ የውሃ ችግር የተከሰተው በዩኒቨርስቲው ውስጥ ብቻ ሳይሆን በከተማው ሁሉ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ዩኒቨርስቲው ለሃያ ሺ ተማሪዎች ውሃ የሚያቀርበው የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር ጭምር ነው ብለዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ውሃ የለም መባሉ ግነት ነው ያሉት አቶ ታጉ፣ ያለውን ውሃ አብቃቅተን ለማዳረስ ብንሞክርም በተለያዩ ምክንያቶች እጥረት ተከስቷል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የአቃቂ ግቢ ተማሪዎችም የውሀ ችግር እየተባባሰ መሆኑን ገልፀው፤ በአቃቂ አካባቢ ውሀ እያለ ግቢ ውስጥ ግን በሦስት ቀንም እንደልብ አይገኝም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታረቀኝ ታደሰ፣ የውሀ ችግር መኖሩን ጠቅሰው፣ ውሃ ለበርካታ ቀናት ይቋረጣል መባሉ የተሳሳተ መረጃ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለሰአታትም ሲሆን ውሀ መቋረጥ እንደሌለበት ዩኒቨርስቲው ያምናል ያሉት ዶ/ር ታረቀኝ፤ ውሀ ሁሌ እንዲኖረን ማድረግ የሚችሉት የውሀና ፍሳሽ ተቋማት ናቸው፤ በበኩላችን ችግሩን ለመቅረፍ አመቺ ቦታ መርጠን፤ ለቦታው ካሳ ከፍለን የውሀ ማከማቻ ታንከር በማስቀመጥ ውሃ እንዳይቋረጥ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የውሃ ጉድጓድ ለመጠቀም ሶስት የውሃ መሳቢያ ሞተሮች አስመጥተናል ብለዋል፡፡

Published in ዜና

በርካታ ሰዎች ተደብድበዋል በላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ከ70 በላይ ሰዎች ታስረዋል

በሳኡዲ አረቢያ በኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያና እንግልት ለመቃወም በትላንትናው እለት ሰማያዊ ፓርቲ ጠርቶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በፀጥታ ሀይሎች የከሸፈ ሲሆን፤ ለሰልፉ የወጡት ሰዎች፣ መንገደኞች፣ በተለያየ ምክንያት ጥቁር የለበሱና ሌሎችም ድብደባ ደርሶባቸዋል፡፡ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከሰባ በላይ ሰዎች በላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ታስረዋል፡፡

በድብደባው ሲቪል የለበሱ የፀጥታ ሃይሎችም እንደተጐዱ የላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ሀላፊ ገልፀዋል፡፡ ሰልፉን የጠራው ፓርቲ አመራሮች ከፅፈት ቤታቸው ሳይወጡ መታሰራቸው የተሰማ ሲሆን የሳኡዲ አረቢያ ኤምባሲ አካባቢ በፌደራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ተከቦ ውሏል፡፡ ወደ ኤምባሲው የሚጠጋ፣ ሰብሰብ ብሎ የቆመ፣ ፎቶ ሲያነሳ የተገኘና ሌሎችም በፖሊስ ነጭ ፒክ አፕ መኪና እየተጫኑ ላንቻ አካባቢ በሚገኘው የወረዳ 18 ፖሊስ የተወሰዱ ሲሆን፤ ፖሊስ ጣቢያ ከገቡት ውስጥ የ70 አመት አሮጊት እና የ62 አመት አዛውንት ይገኙበታል፡፡

“ምንም የማውቀው ነገር የለም፤ ከልጄ ጋር መንገድ እየሄድኩ ነው የተያዝኩት” ብለዋል፤ የ70 ዓመቷ አሮጊት፡፡ ከታሰሩት መካከል በድብደባ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ኢዮብ አርጋው የተባለ ወጣት፤ አብረውት በታሰሩት ሰዎች ጉትጐታና ለቅሶ ፖሊስ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ወስዶታል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ረቡዕ ማታ በሰጠው መግለጫ፤ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ አራት ዋና ዋና ነገሮች እንደሚከናወኑ ገልፆ ነበር፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጡ ሁሉ በሳኡዲ የሞቱትን፣ የታሰሩትን እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማሰብና ሀዘናቸውን ለመግለጽ ጥቁር እንዲለብሱና ጥቁር ሪቫን ክንዳቸው ላይ እንዲያስሩ፣ ሙስሊሙ በዕለቱ በጁምአ ሶላት እንዲፀልይ እንዲሁም፣ በሳኡዲ ኤምባሲ በር ላይ ተቃውሞ ከመሰማቱ በፊት ለሞቱት የህሊና ፀሎት ለማድረግና በሳኡዲ አረቢያ እየደረሰ ስላለው አጠቃላይ ጉዳት የሚያትት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ጽሑፍ ቀርቦ ሰልፉ እንደሚበተን ገልፆ ነበር።

ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ ፓርቲው ለከተማው መስተዳድር በደብዳቤ ማሳወቁን እና መስተዳድሩ ምላሽ አለመስጠቱን፤ ይህ ደግሞ ሰልፉ መፈቀዱን የሚያሳይ እንደሆነ ኢ/ር ይልቃል ቀደም ብለው ገልፀው ነበር፡፡ የፓርቲው አባላት እንደገለፁት፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃልን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ለሰልፉ ከፓርቲው ጽ/ቤት ሳይወጡ ነው በፖሊስ የተወሰዱት፡፡ በስፍራው ተገኝተን እንደታዘብነው “ልጆቻችን ታረዱ ተገደሉ” እያሉ የሚያለቅሱ እናቶች የነበሩ ሲሆን “ፖሊስ በህዝቡ ላይ ድብደባና እንግልት ማድረሱ አግባብ አይደለም፤ ይህ ኢትዮጵያ ሳይሆን ሳኡዲ ማለት ነው” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ “ፎቶ አንስታችኋል” በሚል ከሌሎች ሰዎች ጋር በፖሊስ ተይዘው ወረዳ 18 ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ከስድስት ሰዓት እስከ ስምንት ተኩል ቆይተዋል፡፡

በፖሊስ ጣቢያው ውስጥ ከነበሩት መካከል አብዛኞቹ መንገደኞችና ስለጉዳዩ ምንም እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ ጋዜጠኞች ብቻ ተጠርተን የጣቢያው ሃላፊ ያነጋገሩን ሲሆን፤ “ሰልፉ አልተፈቀደም፣ ህገወጥ ነው፤ ህዝቡ ኤምባሲውን ሰብሮ ሊገባ ሲል ዝም ብሎ ማየት አይቻልም፣ ነገሩን በክፉ አትዩት ጉዳዩን የኢትዮጵየ መንግስትና የአለም መንግስታት እየተከታተሉት ነው” በማለት ካሜራችንን እና መታወቂያችንን የመለሱልን ሲሆን አንድ ጋዜጠኛ በሞባይሉ ያነሳውን ፎቶ እንዲያጠፋ ተደርጐ ተለቀናል፡፡ ፖሊስ ጣቢያው ውስጥ የነበሩ ከ70 በላይ ሰዎች ማተሚያ ቤት እስክንገባ ድረስ በእስር ላይ እንደነበሩ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ዜና

በኢትዮጵያ ያለው የመንግስት ስርአት በርካታ ጋዜጠኞችን እስር ቤት አጉሯል፣ ጠንካራ የግል ጋዜጦችንም ዘግቷል ያለው አንድነት ፓርቲ፤ የሚዲያ ነፃነት እንዲረጋገጥና፣ የታሰሩ ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠየቀ፡፡ ፓርቲው ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተዘጋጀው ስድስተኛው የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ፎረም ላይ የተገኙ የሚዲያ ባለቤቶችና አዘጋጆች፤ በሀገሪቱ ስላለው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ችግር፣ ስፋትና ጥልቀት፣ ቃሊቲ ሄደው የታሰሩ ጋዜጠኞችን በማነጋገር ማረጋገጥ ይችላሉ ብሏል፡፡

ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱን እንዳልተቃወመ የጠቆመው ፓርቲው፣ በገዢዎች የሚታፈነው የአፍሪካ ሚዲያ ላይ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ ግን የለኝም ብሏል፡፡ ሚዲያውን የሚጨቁኑትና የሃሳብ ልዕልና እንዳይኖረው የሚያደርጉት አምባገነን መሪዎች መሆናቸውን በመግለፅ፡፡ “በኢትዮጵያ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ተልካሻ ሰበብ እየተፈለገ ይዘጋሉ፤ ሥርዓቱን የሚተቹ ጋዜጠኞች አገር ጥለው እንዲሰደዱ ይደረጋሉ፤ ወደ እስር ቤትም ይወረወራሉ” ያለው ፓርቲው፤ በተለይ የነፃው ፕሬስ በመንግስት የተቀነባበረ ከፍተኛ ጥቃት ይፈፀምበታል ብሏል፡፡

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ፎረም መጠናቀቅ ተከትሎ “በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ታስረዋል” የሚለውን የተሳታፊዎች የጋራ አቋም በመቃወም በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ሶስት የጋዜጠኞች ማህበራት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ “አንድም ጋዜጠኛ በሙያው ምክንያት አልታሰረም፤ የፕሬስ ነፃነት ከማንኛውም የአፍሪካ አገራት በተሻለ ተከብሯል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

ዩኒቨርስቲዎች የውሃ እጥረት ለማቃለል እየጣርን ነው ብለዋል

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በውሃ እጦት ረቡዕ እለት ሰልፍ ከወጡ በኋላ በርካታ ተማሪዎች የታሰሩ ሲሆን፤ ለሦስት ሳምንት ውሃ መቋረጡን በመቃወም የተሰበሰቡ የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የግቢው ጥበቃ እንደበተናቸው ተገለፀ፡፡ በአቃቂ የሚገኘው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በውሀ እጦት መቸገራቸውንና ሰሚ ማጣታቸውን ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲዎቹ አስተዳደሮች በበኩላቸው፤ ውሃ ጨርሶ ጠፍቷል መባሉ የተጋነነ አባባል ነው በማለት፣ የውሃ እጥረት ለማቃለል እየጣሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በውሃ እጦት የተነሳ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳካሄዱ የተናገሩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ረቡዕ ማታ የከተማዋ ፖሊስ የዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በመግባት በርካታ ተማሪዎችን እንዳሰረ ገልፀዋል፡፡ በማግስቱ የተወሰኑ ተማሪዎች ከእስር መለቀቃቸውንና ግቢው መረጋጋቱም ተነግሯል፡፡

ውሃ ካጣን ሦስት ሳምንት ሆኖናል የሚሉት የአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ የዩኒቨርስቲ አስተዳደር መፍትሔ ሊሰጠን አልሞከረም ብለዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች ተሰባስበው ሁለት ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲሞክሩ በግቢው ፖሊሶች እንደተበተኑ ተማሪዎቹ ጠቅሰው፤ አንድ ጄሪካን ውሃ ለመቅዳት ከሶስት ሰዓት በላይ ለወረፋ እንቆማለን ብለዋል፡፡ በሁለት ቀን አንዴ ውሃ ታገኛላችሁ ተብለን በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ፕሮግራም ቢለጠፍም፤ በተባለው ቀን ውሃ አግኝተን አናውቅም ያሉት ተማሪዎቹ፤ ለንጽህና ቀርቶ የመጠጥ ውሃ የምናገኘው በግዢ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርስቲው የአለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ታጉ ዘርጋው፤ የውሃ ችግር የተከሰተው በዩኒቨርስቲው ውስጥ ብቻ ሳይሆን በከተማው ሁሉ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ዩኒቨርስቲው ለሃያ ሺ ተማሪዎች ውሃ የሚያቀርበው የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር ጭምር ነው ብለዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ውሃ የለም መባሉ ግነት ነው ያሉት አቶ ታጉ፣ ያለውን ውሃ አብቃቅተን ለማዳረስ ብንሞክርም በተለያዩ ምክንያቶች እጥረት ተከስቷል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የአቃቂ ግቢ ተማሪዎችም የውሀ ችግር እየተባባሰ መሆኑን ገልፀው፤ በአቃቂ አካባቢ ውሀ እያለ ግቢ ውስጥ ግን በሦስት ቀንም እንደልብ አይገኝም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታረቀኝ ታደሰ፣ የውሀ ችግር መኖሩን ጠቅሰው፣ ውሃ ለበርካታ ቀናት ይቋረጣል መባሉ የተሳሳተ መረጃ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለሰአታትም ሲሆን ውሀ መቋረጥ እንደሌለበት ዩኒቨርስቲው ያምናል ያሉት ዶ/ር ታረቀኝ፤ ውሀ ሁሌ እንዲኖረን ማድረግ የሚችሉት የውሀና ፍሳሽ ተቋማት ናቸው፤ በበኩላችን ችግሩን ለመቅረፍ አመቺ ቦታ መርጠን፤ ለቦታው ካሳ ከፍለን የውሀ ማከማቻ ታንከር በማስቀመጥ ውሃ እንዳይቋረጥ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የውሃ ጉድጓድ ለመጠቀም ሶስት የውሃ መሳቢያ ሞተሮች አስመጥተናል ብለዋል፡፡

Published in ዜና

ጋዜጠኛ ነኝ በማለት አጭበርብሯል የተባለው ቻይናዊ የዜድቲኢ ሰራተኛ ነው ተብሏል። ZTE፣ ለስራ ወደ ጅማ የሄደ ሰራተኛ የለንም፤ የተፈላጊውን ማንነት አጣራለሁ ብሏል። በጅማ ከተማ ጋዜጠኛ ነኝ በማለት አጭበርብሯል የተባለው ቻይናዊ ኢንጂነር ዋንግ ዮንግ ለምርመራ እየተፈለገ ሲሆን፣ የጅማ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ከአዲስ አበባ ይዞ ለመውሰድ እያፈላለገ ነው።

ዋንግ ዮንግን በሚመለከት የዜድቲኢ የህዝብ ግንኙነት ተወካይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ዜድቲኢ ለስራ ወደ ጅማ የላከው ሰራተኛ፤ የለም፤ የተፈላጊውን ማንነት እናጣራለን ብለዋል። ከጅማ ፖሊስ ለቀረበ ጥያቄ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ፣ ዋንግ ዮንግ የቴሌኮም ኢንጂነርና የዜድቲኢ ሰራተኛ መሆኑን ገልጿል። የጅማ ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር ተፈላጊውን ተጠርጣሪ ለመያዝ ሲያፈላልግ እንደቆየና ትናንት የዜድቲኢ ተወካዮችን እንዳነጋገረ ታውቋል።

ፖሊስ ዋንግ ዮንግን ለምርመራ ማፈላለግ የጀመረው፣ ጥቅምት አጋማሽ ላይ ጅማ ውስጥ “ጋዜጠኛ ነኝ በማለት አጭበርብሯል” የሚል ጥቆማ ከአካባቢው ነዋሪ ከወ/ሮ ታደለች ተመስገን ከደረሰው በኋላ ነው። ጉዳዩም ከካሳ ክፍያ ጋር መያያዙ፣ ከኩባንያዎች ተቀናቃኝነት ጋር የተሳሰረ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ። ወ/ሮ ታደለች ተመስገን፣ ከሁለት ወራት በፊት ስራ ላይ በአደጋ ህይወቱን ያጣ ሰራተኛ ቤተሰብ ናቸው። የአንድ የአገር ውስጥ ድርጅት ተቀጣሪ የነበረው ሰራተኛ በኢንተርኔት ማስፋፊያ ፕሮጀክት የፋይበር ኦፕቲክስ ዝርጋታ ላይ ነው በአደጋ የሞተው።

የሰራተኛው አሟሟት ላይ ጥያቄዎች ተነስተው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ቀጣሪው ድርጅት በበኩሉ፤ ሰራተኛው አስፈላጊ የጥንቃቄ አልባሳትና መሳሪያዎችን ሲጠቀም እንደነበር በፖሊስ ምርመራ መረጋገጡን ገልጿል። ከሟች ቤተሰብ ጋር በመነጋገር ቀጣሪው ድርጅት የመቶ ሺ ብር ካሳ የከፈለ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን በበላይነት የሚመመራው ሁዋዌ በበኩሉ 200 ሺ ብር ድጋፍ እሰጣለሁ ብሏል። ከዚህ በኋላ ነው፣ ዋንግ ዮንግ ወደ ጅማ መጥቶ “ጋዜጠኛ ነኝ በማለት አጭበርብሯል” የተባለው።

ቻይናዊው ዋንግ ዮንግ መጥቶ እንዳገኛቸውና ሆቴል ድረስ ጠርቶ እንዳነጋገራቸው የጠቀሱት ወ/ሮ ታደለች፣ “ጋዜጠኛ ነኝ፤ ተጨማሪ ገንዘብ እንድታገኙ አደርጋለሁ፤ አዲስ አበባ እንሂድ” በማለት ሊያግባባቸው እንደሞከረ መናገራቸውን ምንጮች ገልፀዋል። ወ/ሮ ታደለች ለፖሊስ ያመለከትኩት ጥርጣሬ ስላደረብኝ ነው ማለታቸው የተገለፀ ሲሆን ፖሊስ በበኩሉ፤ ዋንግ ዮንግ ጋዜጠኛ ሳይሆን የቴሌኮም ኢንጂነርና የዜድቲኢ ሰራተኛ መሆኑን ያረጋገጠው ባለፈው ሳምንት ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባገኘው መረጃ ነው ተብሏል። በእነዚህ መረጃዎች የተነሳ፣ ጉዳዩ በዜድቲኢ እና በሁዋዌ መካከል ካለው ተቀናቃኝነት ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሬ መፈጠሩ አልቀረም። የዜድቲኢ የህዝብ ግንኙነት ተወካይ ስለ ዋንግ ዮንግ ትናንት ተጠይቀው በሰጡን ምላሽ፣ ዜድቲኢ ለማንኛውም ስራ ወደ ጅማ የላከው ሰራተኛ እንደሌለ እርግጠኞች ነን፤ የሰውዬውን ማንነት አጣርተን እናሳውቃለን ብለዋል።

Published in ዜና

ከገቢዎችና ጉምሩክ የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩት ባለሀብቶች መካከል የምፋሞ ትሬዲንግ ባለቤት የአቶ ምህረተአብ አብርሃና ኩባንያቸውን ጉዳይ የመረመረው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት፤ ጉዳያቸው የሙስና ክስ ባለመሆኑ በሌላ ችሎት እንዲታይ ሲል ከትናንት በስቲያ ብይን ሰጠ፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ፤ በአቶ ምሕረተአብ አብርሃና ኩባንያቸው ምፋሞ ትሬዲንግ ኃላፊ. የተ የግ. ኩባንያ ላይ አምስት ክሶች ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን በጥቅሉ የክሶቹ ይዘት ኩባንያው ከ1998 እስከ 2004 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ መክፈል የነበረበትን 3.5 ሚሊዮን ብር የመንግስት ገቢ ግብር አልከፈለም፤ ስራ አስኪያጁ አቶ ምሕረተአብም ጉዳዩን ተከታትለው አላስፈፀሙም የሚል ነበር፡፡ ክሱን ተከትሎ የተከሣሽ ጠበቃ ለፍ/ቤቱ ባቀረቡት መቃወሚያ፤ ክሶቹ የሙስና አይደሉም፣ የገቢ ግብር አዋጅን የተመለከቱ ናቸው ያሉ ሲሆን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ የሙስና ክስ ባይሆንም ከገቢዎችና ጉምሩክ በተሠጠኝ ውክልና ነው ክሱን ያቀረብኩት ብሏል፡፡

በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ከትናንት በስቲያ የዋለው ችሎትም፤ በተከሣሽ ጠበቃ በኩል የቀረቡትን ምላሾችና ችሎቱ በጉዳዩ ላይ ያለውን ስልጣን መመርመሩን አስታውቆ፤ 15ኛ ወንጀል ችሎት ከ10 አመት በላይ የሚያስቀጡ የሙስና ወንጀሎችን ብቻ እንዲመለከት ስልጣን የተሠጠው መሆኑን አመልክቷል፡፡ ፍ/ቤቱ በሰጠውም ብይን፤ ጉዳዩ የሙስና አለመሆኑን አቃቤ ህግ ራሱ ያረጋገጠው በመሆኑና 15ኛ ወንጀል ችሎት የሙስና ያልሆኑ ጉዳዮችን የማየት ስልጣን ስለሌለው፣ የአቶ ምህረተአብ አብርሃ ጉዳይ በሌላ ችሎት እንዲታይ አዝዟል፡፡

በተከሣሽ ጠበቃ የቀረቡት ሌሎች የመቃወሚያ ነጥቦችም ጉዳዩን እንዲመለከት ስልጣን በተሰጠው ችሎት በኩል የሚታይ እንደሆነ ፍ/ቤቱ አስታውቋል፡፡ ባለሃብቱ አቶ ምሕረተአብ አብርሃ፤ በሽግግር መንግስቱ ወቅትና ከዚያ በኋላ የሃገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት የአቶ ስዬ አብርሃ ወንድም ሲሆኑ፤ በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፋንታን ጨምሮ የመ/ቤቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ባለሀብቶች በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ሲታሰሩ አብረው የታሠሩ ናቸው፡፡

Published in ዜና

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾችን (ዋልያዎቹን) ለመደገፍ ባለፈው ረቡዕ ከባለቤቱ አምለሰት ሙጬ ጋር ወደ ካላባር ናይጄርያ የተጓዘው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን፤ ከጨዋታ መልስ የጀግና አቀባበል ይገባቸዋል አለ፡፡ ከሳምንት በፊት “መሬት ሲመታ” የተሰኘውን ሙዚቃ ቪድዮ ለዋልያዎቹ በመስጠት ለአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው መፅሃፍት ያበረከተው ቴዲ አፍሮ፤ ሙዚቃውን የሰራው አድናቆቱን ለመግለጽና ለማበረታታት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የሙዚቃው ግጥምና ዜማ የቴዲ አፍሮ ፈጠራ ሲሆኑ፣ የሙዚቃ ቪዲዮውን ያዘጋጀችው ባለቤቱ አምለሰት እንደሆነች ይታወቃል፡፡

ቴዲ አፍሮ ከዋሊያዎቹ ጋር ሲገናኝ የሰሞኑ ጉብኝት የመጀመሪያው እንዳልሆነ የገለፁት የድምፃዊው ተወካይ ጌታቸው ማንጉዳይ፤ አምኖ ዋልያዎቹ የቴዲ አፍሮ ተጋባዥ እንግዶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ ብሔራዊው ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በመጨረሻው ጨዋታ ዋዜማ ቴዲ አፍሮ በጊዮን ሆቴል ባዘጋጀው ኮንሰርት “ብታሸንፉም ባታሸንፉም የክብር እንግዶቼ ናችሁ” ብሎ ዋልያዎቹን ጋብዟቸው ኮንሰርቱን ታድመዋል።

በዋሊያዎቹ ስኬት መደነቁንና መመሰጡን ቴዲ አፍሮ ገልፆ፤ ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በተሳተፉበት ወቅት ኮንሰርት እንዳቀረበና ከዛምቢያ ጋር ያደረጉትን የመክፈቻ ጨዋታ ስታድዬም ገብቶ እንደተመለከተ ይናገራል። ከ5 ወር በፊትም በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባካሄዱት የባህልና ስፖርት ፌስቲቫል ላይ ኮንሰርት ሲያቀርብና ከሙዚቃ ከባንዱ ጋር የዋሊያዎችን ማልያ ለብሶ ለስኬታቸው አድናቆቱን አሳይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ በታየበት የስፖርት መድረክ ሁሉ ልዩ ክብርና ኩራት ይሰማኛል ያለው ቴዲ አፍሮ፤ “ዋልያዎቹ በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን አንድ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ አዲስ ተስፋም ፈጥረዋል። በማንኛውም ውጤት ወደ አገራቸው ሲመለሱ የጀግና አቀባበል ይገባቸዋል ብሏል - ቴዲ አፍሮ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ በኮካ ኮላ ኩባንያ ለቀጣዩ የፊፋ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ከሚያሰሩ ይፋዊ ዘፈኖች መካከል የአፍሪካውን ድርሻ እንዲሰራ መመረጡ መመረጡ የሚታወቅ ሲሆን፤ የዘፈኑ ቀረፃ በኬንያ ተከናውኖ ሲሆን በቅርቡ በመላው ዓለም ለአድማጮች እንደሚቀርብ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በካላባር ከተማ ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ባለፈው ረቡዕ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻርተር አይሮፕላን ከተጓዙት 215 ኢትዮጵየውያን መካከል፤ 60 ያህሉ የዋልያ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ለአውሮፕላን ትኬት 28ሺ ብር የከፈሉት ደጋፊዎች፣ በናይጄሪያ ቆይታቸው ወደ 40ሺ ብር ገደማ ወጪ እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡

Published in ዜና

ከ52 የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ 33ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች

ከ11 የምስራቅ አፍሪካ አገራት ደግሞ በ8ኛ ላይ ተቀምጣለች

መልካም አስተዳደር ከ100%

  • ሞሪሺየስ - 80
  • ቦትስዋና - 78
  • ኬፕቨርዴ - 77
  • ሲሸልስ - 78
  • ደቡብ አፍሪካ - 71
  • ሶማሊያ - 8

የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የ2013 የመልካም አስተዳደር ውጤታማነት ደረጃን “Ibrahim Index of African Governance (IIAG)” ይፋ ያደረገው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር፡፡ በመልካም አስተዳደር ምርጥ ተብላ ከአፍሪካ በአንደኝነት ደረጃ የተቀመጠችው ሞሪሺየስ ስትሆን የመጨረሻዋ አገር ሶማሊያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከ52 የአፍሪካ አገራት 33ኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን የመልካም አስተዳደር ሁኔታ በአራት መስፈርቶች የገመገመው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን፤ ባለፉት 10 ዓመታት በሰው ሃብት ልማት ላይ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ገልፆ፤ በዋናነት በጤና እና በትምህርት መስኮች ለውጥ መመዝገቡን አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በመልካም አስተዳደር ከ52 የአፍሪካ አገራት 33ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ከ100 ነጥብ 47.6 በማግኘት ሲሆን የአፍሪካ አማካይ ነጥብ 51.6 ነው ይላል ፋውንዴሽኑ፡፡

ኢትዮጵያ ከ11 የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ተወዳድራም በ8ኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠች የጠቆመው የፋውንዴሽኑ መረጃ፤ በዚህ የአፍሪካ ቀጠናም ኢትዮጵያ የሚጠበቀውን የ47.9 አማካይ ነጥብ አለማግኘቷን አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት በመልካም አስተዳደር ያላትን ደረጃ ያሻሻለችው በ5.1 ብቻ ነው ይላል፤ መረጃው፡፡ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን “ኢብራሂም ኢንዴክስ ኦፍ አፍሪካን ጋቨርናንስ” ሪፖርት፤ የአፍሪካ አገራት በአጠቃላይ በመልካም አስተዳደር መሻሻል እንዳሳዩ ጠቁሟል፡፡ አገራቱ የተመዘኑት የመልካም አስተዳደር መገለጫ ናቸው ተብለው በሚታወቁት የዜጎች ደህንነት እና የህግ የበላይነት፣ ህዝባዊ ተሳትፎ እና ሰብዓዊ መብት አከባበር እንዲሁም ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድሎችና በሰው ሃብት ልማት እንደሆነ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከ1 ቢሊዮን በላይ ከሚገመተው የአፍሪካ ህዝብ ውስጥ 94 በመቶ ያህሉ የሚኖሩት በመልካም አስተዳደር መሻሻል ባሳዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ እንደሆኑ ታውቋል። ሆኖም በተለይ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ በዲሞክራሲ እና በሰብዓዊ መብት አከባበር የሚታየው ድክመት፣ ሁሉን ነገር ወደኋላ እየጎተተ ነው ተብሏል፡፡ በመልካም አስተዳደር በአፍሪካ ምርጥ ተብላ በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠችው ሞሪሽዬስ ስትሆን ቦትስዋናና ኬፕ ቨርዴ፤ ሲሸልስ እና ደቡብ አፍሪካ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ወስደዋል፡፡

ባለፉት 13 ዓመታት 52 የአፍሪካ አገራት በጥቅሉ በመልካም አስተዳደር መሻሻል እንዳሳዩ የሚገልፀው ሪፖርቱ፤ በተለይ ጠንካራ መሻሻል የታየው በሰው ሃብት ልማት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ በኢኮኖሚ መስክ ዘላቂ ዕድሎች መፈጠራቸው በመላው አህጉሪቱ የሚታይ አበረታች ክስተት እንደሆነም ይገልፃል። በመላው አፍሪካ ዝቅተኛ መሻሻል እየታየ ያለው በሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና በህግ የበላይነት ዙሪያ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ እነዚህ የመልካም አስተዳደር መገለጫዎች በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአሳሳቢ ሁኔታ እያሽቆለቁሉ ናቸው ሲል አስጠንቅቋል፡፡ በህግ የበላይነት ያለው የመንግስታት አፈፃፀም በየጊዜው እየወረደ መምጣቱን በመግለፅም የተሻሉ የሚባሉት ከ54 አገራት 20ዎቹ ብቻ እንደሆኑ ሪፖርቱ ጠቅሷል። አፍሪካ የዜጎቿን ደህንነት በመጠበቅ በኩል ምቹ እንዳልሆነችም ይገልፃል፡፡ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የ2013 የመልካም አስተዳደር ውጤታማነት ደረጃ ይፋ በተደረገበት ወቅት ዶክተር ሞ ኢብራሂም ባደረጉት ንግግር፤ ሽልማቱ ለላቀ የአመራር ብቃት የሚሰጥ ክብር እንጂ መጦርያ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ “ዛሬ አፍሪካ ለራሷ ችግሮች በቂ መፍትሔ እንዳላት እምነቴ ነው” ብለዋል።

“አፍሪካ ፀለምተኛም ሆነ ተስፈኛ መሆኗን ማሰብ ለአህጉሪቷ ዘመናዊ የእድገት እና የለውጥ ዘመን የሚያመጡት አንዳችም ፋይዳ የለም፡፡ አሁን ዘመኑ የአፍሪካ እውነታን የምንጋፈጥበት ነው፡፡ አህጉራችንን ፊት ለፊት ልንመለከታት ይገባል፡፡ ስኬቶቿን ማድነቅ ተገቢ ነው፤ ጎን ለጎን ግን የወደፊት ፈተናዎቿን ተገንዝቦ ለውጥ በሚያመጣ አቅጣጫ መጓዝ ይገባል” በማለት ዶክተሩ ለአፍሪካ መሪዎች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በአፍሪካ በብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት በኩል መሻሻል እየታየ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ አገራት በአዋሳኝ ድንበሮቻቸው እሰጥ አገባ እና ግጭት መፍጠራቸው እየቀረ መምጣቱ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ለውጥ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ ከአፍሪካ ህዝብ ሲሶው ከ25 ዓመት ዕድሜ በታች እንደሆነ በማመልከትም የዜጎችን ደህንነት በማረጋገጥ እና በህግ የበላይነት በመገዛት ረገድ አገራት መዳከማቸው በውስጥ ችግሮች የሚታመሱበትን ዕድል ያሰፋዋል ሲል አስጠንቅቋል፡፡ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የመልካም አስተዳደር ውጤታማነት ደረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከ1-8 ባለው ደረጃ ላለፉት 10 ዓመታት መቆየት የቻሉት አገራት፡- ሞሪሽዬስ፣ ቦትስዋና ፤ ኬፕ ቨርዴ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲሸልስ፣ ናሚቢያ፣ ቱኒዚያ እና ጋና ናቸው፡፡

ላይቤሪያ፣ አንጐላ፣ ሴራሊዮን፣ ሩዋንዳና ብሩንዲ በግጭት ሲታመሱ ከቆዩበት የመንግስት አስተዳደር ከተላቀቁ በኋላ ባለፉት 10 ዓመታት በመልካም አስተዳደር ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩ የአፍሪካ አገራት መሆናቸውንም ይገልፃል፡፡ ከአንድ እስከ አምስት ያለውን የመሪነት ደረጃ የያዙት አምስት አገራት በመልካም አስተዳደር ከሚሰጠው መቶ ነጥብ ሞሪሽዬስ 83፤ ቦትስዋና 78፤ ኬፕቨርዴ 77፤ ሲሸልስ 75 እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ 71 ነጥብ አስመዝግበዋል፡፡ በመጨረሻው ደረጃ ላይ የምትገኘው ሶማሊያ ከ100 ያገኘችው ስምንት ነጥብ ብቻ ነው፡፡ በአራቱ የመልካም አስተዳደር መለኪያዎች የሁሉም አፍሪካ አገራት አማካይ ነጥብ 51.6 ከመቶ ነው። የሰው ሃብት ልማት 52፤ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድሎች 45፤ በሰብዓዊ መብት 35፤ በዜጐች ደህንነት እና በህግ የበላይነት 20 ነው፡፡ አፍሪካን በአምስት ዞን ከፍለን በመልካም አስተዳደር የተሰጣቸውን ደረጃ ብንመለከት ደቡባዊ የአፍሪካ ቀጠና 59.2 ከመቶ በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ሰሜናዊ አፍሪካ 55 ከመቶ፤ ምስራቅ አፍሪካ 52.5 ከመቶ፤ መካከለኛው አፍሪካ 52.5 ከመቶ እንዲሁም መካከለኛው አፍሪካ 40.1 ከመቶ በማስመዝገብ ከሁለተኛ እስከ መጨረሻ ያሉትን ደረጃዎች አግኝተዋል፡፡

በመልካም አስተዳደር እጦት በመዳከር ላይ እንደሆኑ የተጠቀሱት ደግሞ ዚምባቡዌ፣ ኢኳቶርያል ጊኒ፣ ቻድ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐና ሶማሊያ ናቸው። በሰብዓዊ መብት አከባበር፣ ሃሳብን በመግለጽ ነፃነት፣ በአስከፊ ወንጀሎች፣ በማህበራዊ ቀውሶች እና አለመረጋጋት፣ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በአገር ውስጥ የእርስበርስ ግጭቶች፤በአወዛጋቢ የስልጣን ሽግግሮች፣ በባንኮች ግልጽ አሰራር እጦት፣ በዜጐች እና በሠራተኞች መብት አከባበር የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የአፍሪካ አገራት በዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ላይ እንዳይሰሩ ፈተና ሆነው መጋረጣቸውንም ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ የሞ ኢብራሂም ሽልማት የ7 ዓመታት ጉዞ ዶክተር ሞ ኢብራሂም የ67 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ የሱዳንና የእንግሊዝ ጥምር ዜግነት ያላቸው ባለሃብት ናቸው፡፡ ሞ ኢብራሂም፤ በግል ጥረታቸው የቢሊዬነርነት ደረጃ ላይ የደረሱ ስራ ፈጣሪ ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ ያላቸው ሃብት ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ፎርብስ መፅሄት ይጠቁማል፡፡ በ1998 እ.ኤ.አ በኮሙኒኬሽን ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩት፤ በአፍሪካ “ሴልቴል” የተባለ የመጀመርያውን የግል የሞባይል ቀፎ አምራች ኩባንያ የመሰረቱት ሲሆን በ23 የአፍሪካ አገራትና በመካከለኛው ምስራቅ ሰፊ ገበያ እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡ በ2005 እ.ኤ.አ ይህን ኩባንያቸውን በ3.4 ቢሊዮን ዶላር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽንን በማቋቋም በአፍሪካ አገራት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ፋውንዴሽኑ፤ የሞ ኢብራሂም የመልካም አስተዳደር ሽልማትን በመስጠት፤ የአፍሪካ አገራትን አመታዊ የመልካም አስተዳደር ውጤታማነት ደረጃ በማውጣት እና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ፎረም በመምራት ይንቀሳቀሳል፡፡ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በመልካም አስተዳደር ለሚያሳዩት የላቀ ብቃት የሚበረከተው የሞ ኢብራሂም ሽልማት የተጀመረው የዛሬ 7 ዓመት ገደማ ነው፡፡ ሽልማቱ በአፍሪካ በስልጣን ዘመናቸው ለአገራቸው እና በአጠቃላይ ለአህጉሪቱ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ እና የለውጥ ተምሳሌት ለሆኑ የቀድሞ መሪዎች እውቅና የሚሰጥበት ነው፡፡ ሽልማቱ ገለልተኛ እና ታዋቂ በሆኑ የአፍሪካ ምሁራንና ፖለቲከኞች የተዋቀረ ኮሚቴ በሚያካሂደው ምርጫ መሠረት የሚሰጥ ሲሆን በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ሁለት የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎችም ይገኙበታል፡፡ የኢብራሂም ሽልማት የሚሰጠው በአገራቸው የልማት ጉዞ የላቀ ሚና ለተጫወቱ፣ ህዝቦቻቸውን ከድህነት አረንቋ በማውጣት በዕድገት እና ለውጥ ጐዳና ለተጓዙ፣ ለተሻለ ህይወት እና ብልጽግና የሚያበቃ አመራር ለሰጡ፤ በአህጉር ደረጃ በተምሳሌትነት የሚታይ ብቁ አመራር ላሳዩ የአፍሪካ መሪዎች ብቻ ነው፡፡ የሞ ኢብራሂም ሽልማት አሸናፊዎች፤ በመንግስት አመራር ላይ ሳሉ የነበራቸውን ብቁ የአመራርነት ሚና ከስልጣናቸው ወርደውም እንዲገፉበት እና ያካበቱትን ልምድ እንዲሰሩበት ያበረታታል፡፡

የሞ ኢብራሂም ሽልማት የሚሰጠው፤ በአገሩ የመንግስት ስርዓት ከፍተኛው ስልጣን ላይ ላገለገለ፤ ከስልጣን ከወረደ ቢያንስ 3 ዓመት ላለፈው፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ በመመረጥ አገሩን ሲመራ ለቆየ፤ የአገሩን ህገመንግስት አክብሮ በአግባቡ የስልጣን ጊዜውን ላጠናቀቀ እና በስልጣን ቆይታው እንደተምሳሌት ለመታየት የሚያስችል የመሪነት ብቃት እንደነበረው ለተረጋገጠለት መሪ ብቻ ነው፡፡ የሞ ኢብራሂም ሽልማት አሸናፊ ሆኖ ለሚመረጥ መሪ የሚበረከትለት የገንዘብ ሽልማት በዓለም በተመሳሳይ ዘርፍ ከሚሰጠው ከፍተኛው ነው፡፡ አሸናፊው አፍሪካዊ መሪ በ10 ዓመታት ውስጥ 5 ሚሊዮን ዶላር ተከፋፍሎ ይሰጠዋል - በየዓመቱ 500ሺ ዶላር ገደማ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም በህይወት ዘመን ቆይታው በየዓመቱ 200ሺ ዶላር የሚሰጠው ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ተሸላሚው በሚያቀርበው የበጐ አድራጐት ፕሮጀክት መሰረት፤ 200ሺ ዶላር ዓመታዊ በጀት ይፈቀድለታል።

የሞ ኢብራሂም ሽልማት የመጀመሪያው አሸናፊ የሞዛምቢኩ ፕሬዚዳንት ጆአኪም ቺሳኖ ነበሩ - በ2007 ዓ.ም፡፡ በቀጣዩ ደግሞ የቦትስዋናው ፕሬዚዳንት ሬስተስ ሁለተኛው ተሸላሚ ሆነዋል። ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ግን ለሞ ኢብራሂም ሽልማት አሸናፊነት የበቃ አፍሪካዊ መሪ ሳይገኝ ቀረ፡፡ በ2011 ዓ.ም የኬፕ ቨርዴው ፕሬዚዳንት ፔድሮ ፔሬስ፤ ሶስተኛው የሞ ኢብራሂም ሽልማት አሸናፊ ለመሆን ሲበቁ፤ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ በዚያው ዓመት የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ልዩ የክብር ሽልማትን ለማግኘት ችለዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም የሞ ኢብራሂም ሽልማትን ያሸነፈ አፍሪካዊ መሪ ለሶስተኛ ጊዜ ሳይገኝ የቀረ ሲሆን ዘንድሮም ለአራተኛ ጊዜ ለዚሁ ክብር የበቃ መሪ አልተገኘም፡፡ የሞ ኢብራሂም ሽልማት የመልካም አስተዳደር ዓመታዊ ደረጃ ሪፖርትን ማዘጋጀት የተጀመረው በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የቴክኒክ ድጋፍ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በመላው አፍሪካ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በሚደረግ ትብብር ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡

ብዙዎቹ አሃዛዊ መረጃዎች ከአፍሪካ ህዝብ በተለያየ መንገድ (ድምፅ እና አስተያየት) የሚሰበሰቡ እንጂ የየአገራቱ መንግስታት የሚያሰራጩትን ፖሊሲ በመንተራስ የሚሰሩ አይደሉም፡፡ የሞ ኢብራሂም ሽልማት በአፍሪካ አገራት ላለው የመልካም አስተዳደር ስርዓት መዳበር ከሚሰጠው እውቅና ባሻገር በስልጣን ዘመናቸው የላቀ ሚና የነበራቸው የአፍሪካ መሪዎች ከሙስና በፀዳ መንገድ መልካም ስራቸውን እንዲቀጥሉ በማበረታት ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተጨማሪም የአፍሪካ መሪዎች የየአገራቸው ህገመንግስት በሚፈቅደው መሠረት፤ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ለማነሳሳት፣ በብቁ መሪነታቸው ሲያበረክቱ የቆዩትን አስተዋጽኦ በአገራቸውና በአህጉር ደረጃ በመቀጠል ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ለማድረግ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ሞ ኢብራሂም፤ ዓመታዊውን የመልካም አስተዳደር ሪፖርት “ከአፍሪካ ፊት የቆመ መስታወት ነው” ሲሉ ይገልፁታል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Page 12 of 19