ከትርዒት መጀመሪያ ሰአት በፊት ያለው የዝግጅት ጊዜ ሰፊ ነው፡፡ በእለቱ ትርዒት ላይ የማይሳተፍ ማንም ሰው ወደ መድረክ ጀርባ እንዲገባ አይፈቀድለትም። ተዋንያኑ በመልበሻ ክፍላቸው ውስጥ ሽር ጉድ ይላሉ፡፡ ሲገናኙ ተቃቅፈው ይሳሳማሉ፤ ከዚያም ለየብቻ ይንሾካሾካሉ፤ ሁሉም ከደረሱ በኋላ በአንዱ ሰፊ ክፍል ውስጥ ተሰባስበው ይፀልያሉ፤ በጋራ ይመገባሉ፤ በጥልቅ ይወያያሉ፤ ጨዋታ ይደራል፤ ዚቅ ይተረተራል፡፡ በመሀል አዲስ ወሬ ሲሰሙ ይገረማሉ፤ ያዝናሉ ወይም ይፎትታሉ፤ ተያይዘው በሳቅ ፍር…ስ! ይላሉ፡፡ ከመሀላቸው በተለይ በፌዘኝነታቸው የሚወደሱቱ ጨዋታ አዋቂዎቹ ከመድረክ ጀርባም ዘወትር በሰው እንደተከበቡ ነው።
ተዋንያኑ እንዲህ ዘና ባለ ስሜት ውስጥ ሆነው፣ የውጪውን አለም ወዲያ እየተዉ ቀልባቸውን ይሰበስባሉ፤ ከግል ኑሯቸው ሀሳብ እየራቁ ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በጥብቅ ይቆራኛሉ፡፡ ይህ ድርጊታቸው ጊዜ የሚያባክኑበት አጉል ቆይታ ሊመስል ይችላል፤ ግን በአንዳች “መግነጢሳዊ” ሀይል እየተነዱ፣ ከእውኑ ማንነታቸው ተነጥለው ወደሚጠብቃቸው የምናብ አለም የሚነጉዱበት እርስበርስ የመናበቢያና የተመስጦ ጊዜ ነው፡፡ ሰውነታቸውን በስፖርት ያፍታታሉ፤ አይኖቻቸውን ጭፍን ክፍት፣ ግንባራቸውን ጨምደድ ፈታ እያደረጉ፣ ጉሮሯቸውን በስልት ይሞርዳሉ፤ አልባሳትና የፊት ገፅ ቅባቸውን በመስተዋት እያስተዋሉ፣ ቀስ በቀስ ለየብቻ ሆነው በፀጥታ ይቆዝማሉ፡፡ ራሳቸውን ከዕለት ተዕለት ህይወታቸው የሀሳብ ውጣ ውረድ ይገታሉ፡፡ ማንኛውም ለሞያ ስነ ምግባሩ ታማኝ የሆነ ባለሞያ (“የጥበብ ካህን”) እጅግ ከአቅም በላይ የሆነ መፍትሄ አልባ ችግር ካልገጠመው በቀር በዚህ ሰአት ከመድረክ ጀርባ አለመገኘት አይቻለውም፤ ራሱን ያስገዛለት የሞያ ቃል ኪዳኑ ግድ ይለዋልና፡፡ ይህቺን የዝግጅት ጊዜ ሁሉም ይናፍቋታል፤ ለእነርሱም በጣም ጠቃሚና ውድ ጊዜ ናት፡፡
መራሄ ተውኔት እንደመሆኔ፣ ትርዒት ባለ ቀን ቀደም ብዬ ተገኝቼ፤ በቅን የስራ መንፈስ እየተጋገዙ ከሚኖሩት አይሰለቼ የመድረክ ግንባታ ባለሞያዎች የሚጠበቅብኝ የሀሳብ እርዳታ ካለ ምክሬን ለግሼና ምንም የጎደለ ነገር አለመኖሩን አረጋግጬ ሳበቃ፤ ተዋንያኑ ክፍል ጎራ ብዬ ጥርስ አያስከድኔ ጣፋጭ ወጋቸውን ሲጠርቁ፣ ጥቂት አብሬያቸው እቆይና፣ ከመድረክ ጀርባ እንጎራደዳለሁ፡፡ አንዳንዴ ብቻ ወደ አዳራሹ ሄጄ፣ ከፎቁ የኋላ ወንበር መሀል ቆሜ፣ በጨለማ ተውጦ መጋረጃው የተዘጋውን ዝም ያለ መድረክ አፍጥጬ አያለሁ፡፡ ታዲያ በዚህች ደቂቃ በፀጥታ የተዋጠውን አዳራሽና ፅልመት ያጠላበትን የደበዘዘ መድረክ እያስተዋልኩ፣ ለራሴ ፈገግ እላለሁ። የፈገግታዬ ምንጭ ሌላ አይደለም፤ ምክንያቱ ከመድረክ ጀርባ ተዋንያኑ በኋላ በዚህ መድረክ ላይ ምን ሊፈጥሩ እንደሚታትሩ ጠንቅቄ የማውቅ በመሆኔ ነው፡፡ እንደ የመድረክ ጀርባው ውሎና የተዋንያኑ የጥበብ ማዕድ እውቂያዬ ሁሉ፣ ከአዳራሹ ጋር ካለኝ የረዥም አመታት ጥብቅ ቁርኝት የተነሳ፣ ከፊት ወንበሮች ይልቅ አሁን የቆምኩበት አካባቢ ኋላ ወንበሮች ላይ የተቀመጡ ተመልካቾች፣ የተዋንያኑን እንቅስቃሴ በጉልህ ለማስተዋልና ድምፃቸውን ጥርት አድርጎ ለማድመጥ እንደሚቸገሩም አውቃለሁ፡፡ ተዋንያኑም ይህን ችግር ለመቅረፍና ከጥግ እስከጥግ በአዳራሹ ለሚታደሙ ሁሉ ትወናቸው ባግባቡ እንዲታይ ብቁ ሆኖ ለመገኘት ከልምምድ ጊዜ ጀምሮ የፅሙናና ትህትና መቋሚያን ተመርኩዘው፣ አቅል የሚያናውዝ የሚሰኝ አድካሚ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
በአንፀባራቂ መክሊታቸው የሚሳካላቸው ጥቂቶቹ ብቻ የሚያከብሩትን ተመልካች አርክተው፣ የሚያከብራቸው ታዳሚ በመፍጠር፣ ለህይወት ዘመንና ከእረፍታቸውም በኋላ የሚዘልቅ ሀውልት ስማቸውን አኑረው ያልፋሉ፡፡ ያመዛኙ ህልምና የኑሮ አላማም በዚሁ የተቃኘ ሲሆን፤ ሞያውን ከሌሎች ሞያዎች የሚለየውም ይኸው ነው። “ይህን ማድረግ ያልቻለውንማ ሞያዊ የታሪክ ድርሳናት የህያው ግብሩን ፍሬ ከገለባው አንገዋለው፣ ወይኑን አጣጥመው፣ “ካህኑን” አውራ አድርገው ሊቀቡት፣ በአርአያ ሰብዕ ስያሜ ሊያነግሱት፣ ሀውልቱን ሊያቆሙለት ይቻላቸዋልን? ለዚህ ብቃት አለመታደልስ በነጠፈ ክህሎት መድረክ ላይ ቆመው ከሚያነበንቡ እልፍ ተዋንያን በምን ይለያል? ለባለሞያው ለራሱስ ቢሆን በዚህ ተሰጥዖና ብርቱ ፅናት በሚሻ ሞያ ውስጥ በመሆንና በሌላ አይነት ሞያ መተዳደር መሀል መዋዠቁ ምን ለውጥ ያመጣለት ይሆን?” ነው በመላ አካል ደም ስራቸው፣ በተግዳሮት ባልጠለሸ መንፈሳቸው የሰረፀው የሞያ መርህ እምነታቸው፡፡ “በዚህ ሞያ ውስጥ እየኖርኩ ነው የሚል “የጥበብ ካህን” ባለሞያስ፣ ከአበው የወረሰውን የፅናት ጽዋ በድል እስኪቀዳጅ፣ ስለ የሰው ልጆች የእውነት ብስራት ራሱን በተምሳሌትነት ሰውቶ፣ እንደ ሻማ ቀልጦ የሀቅ ወጋገን ቀንዲል ሆኖ ከማለፍ፣ በወረት ተጠልፎ ቢሰናከልና “ክህነቱን” ቢያፈርስ፤ ከጥበብ ጋር በቃልኪዳን የተሳሰረበትን የሞያ ጋብቻውን ተክሊል አሳድፎ፣ የመንፈስ ልዕልናውን አጉድፎ፣ ማተቡን በጥሶ፣ “ጽላቱን” ሸርፎ፣ ለራሱ ስቶ ከሽፎ ስንቱንም አስቶ አክሽፎ፣ ከከበረ እውነቱ በስጋው ፈተና በአለም አዱኛ ተሸንፎ፣ አርምሞውን ፈትቶ፣ በስካር አፉ ስንቱን ጉድ በመለፍለፉ፣ ጾም ፀሎቱን ሱባኤውን በመግደፉ፣ በበግ ለምድ አክሊል መርገፉ፣ በፌሽታ እንኮኮ በመርገፍገፉ፤ ዛሬ፣ ግራ በሚያጋባው ወለፈንዲ ቁመናው፣ በትውልዱ መሀል በአደባባይ የሀቅ ሸንጎ ከመጠየቅ፤ ነግ፣ ከታሪክ ተወቃሽነት ሊድን ይቻለዋልን? አሸሼ ገዳሜው ሰክኖ፣ አረፋ ደፈቅ ስሜቱ እንደ ጤዛ ተንኖ ወደ ቀልቡ ሲመለስ፣ ውሎ ሲያድርስ (ለጊዜ ሳይሆን ለኪዳኑና ለራሱ ታማኝ ከሆነ) በሞያ አሳይ መሲህነቱ እንዴት ነው በህሊናው የማይከሰስ? አምርሮስ እማይፀፀት? ጭራሽ አእምሮው ካልተዛባ ወይ እስከወዲያኛው እንደ እርያ ለከርሱ ብቻ ካላደረ በቀር?” ...

የመጀመሪያው ደወል . . .
መጋረጃ ሊከፈት ሲል ከመድረክ ጀርባ መቆም ተአምር ያሳያል፡፡ የተዋንያኑ የቀጣይ ሦስት ሰአታት ትርዒት የዝግጅት ጊዜ ተጠናቅቋል፡፡ አሁን ሁሉም በተሟላ አልባሳትና የፊት ገጽ ቅብ ተዥጎርጉረው ዝግጁ ሆነዋል፡፡ በራስ መተማመንን ከማጣት ሳይሆን እርግጠኛ መሆንን ከመታበይ በመቁጠር፤ ለሞያው ባላቸው የገዘፈ ክብርና ተመልካች አይን ስር ለመቆም ከመሽቆጥቆጥ ብዛት በጭንቀት ተውጠው፤ (በተለይ በአዲስ ተውኔት መክፈቻ ቀንና ተውኔቱ እስኪልምና እስኪገራ ድረስ ይብሳል) ሳያጣድፋቸው ተጣድፈው አስር ጊዜ መፀዳጃ ቤት እየደረሱ፣ እንትፍታህል ሳይቆዩ እጃቸውን የታጠቡበትን ውሃ በጥድፊያ እያራገፉ፣ ወዲያው ወዲያው የሚመላለሱ አሉ፤ ሌላው አጮልቆ ባየው መድረኩ መሀል ላይ በወደቀች ደማቅ የክር ቁራጭ “ካሁኑ ስሜቴ ተሰረቀ!” ብሎ ያጉረመርም ይሆናል፤ አዲስ በተገዛላት ጫማ መጥበብ የምትነጫነጭ ወይ ባለፈው ሳምንት ትርዒት ላይ የተበጨቀ ክራቫቱን እስካሁን ሳያስተካክል ዘንግቶ ባለቀ ሰአት ሲያየው “ኤጭ!” የሚል ይኖራል፡፡ አንዳንዴም የተመገበው ምግብ ሆዱን እየጎረበጠው ሲያስታምም ቆይቶ፣ እየባሰበት ሲመጣ በኋላ በትርዒት መሀል ከመሰቃየት ብሎ በእንጥፍጣፊ ቅጽበት ላይ ከአንዱ ጥግ ድንገት ቱር ብሎ ሄዶ “ቱርርር!” አድርጎ አስወጥቶ፣ ቱር ብሎ ተመልሶ እፎይ የሚል አይጠፋም፡፡ ከሚያሳስቡት መሀል፣ ለምሳሌ ከባድ ጉንፋን በተለይ በመሪ ተዋናይ ላይ ቢመጣ፤ ስራው (“ቅዳሴ”) እንዳይታጎል ከዋዜማ ቀናቱ ጀምሮ ጉንፋኑ በሰለ አልበሰለ የሁሉም ስጋት ሆኖ ተጥዶ ውሎ ያድራል፡፡ በሌላ ጥግ ደግሞ ከእውኑ ማንነቱ ተነጥቆና ፍጹም የተላበሰውን ገጸ-ባህሪውን ሆኖ በምናብ አለም የሚንሳፈፈፍ ተዋናይ እንደ ቀውስ አይኑን እያጉረጠረጠ ያነበንባል፡፡ እሱን መሰል የተነጠቀች በጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ እንደ ደጋን የተወጠረች ትንፋሷ ቁርጥ ቁርጥ የሚል ተዋናይት፤ ከመድረክ ገጹ ግርግዳ በአንዱ ጀርባ ላይ ተጣብቃ፣ ቶሎ እንዲጀመር ትቃትታለች፡፡ ባንፃሩ ተራቸው እስኪደርስ ዘና ባለ ስሜት በየወንበራቸው ተረጋግተው ተቀምጠው የሚያነብቡና ፈንጠር ፈንጠር ብለው በሹክሹክታ የሚያወጉም አሉ፡፡

ሁለተኛ ደወል...
መብራቱ ሙሉ ለሙሉ ድርግም ብሎ ሲጠፋ፣ የመድረኩ ዙሪያ እርጭታ ያረብበታል፡፡ የመክፈቻ ሙዚቃው ሲጀምር ደሞ የበለጠ ሁሉም በጥልቅ ዝምታ ተሸብበው ስንዝር ሳይላወሱ በያሉበት በተጠንቀቅ ይቆማሉ፡፡ ፀጉራቸውም ይቆማል፡፡ “ተዋናይ የብኾር ቆዳ ነው ያለው” ምናምን ይባላል። በመጀመሪያው ትዕይንት ላይ የሚሳተፉቱ ቀደም ብለው ገብተው መድረክ ላይ ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡ ቀጥለው የሚገቡት ደሞ አልባሳትና የትወና ቁሳቁሶቻቸውን አስር ጊዜ እያስተካከሉ፣ አይናቸውን መድረኩ ላይ ሰክተው ይጠባበቃሉ፡፡ በጨለማው ውስጥ ሳይጠበቅ “የተጣደው ጉንፋን” ከክናፍር ቢያመልጥና ካፊያው ሌላ ተዋናይ ፊት ላይ ቢያርፍስ? ድንገት ከመድረክ ጫፍ ቁልቁል ተፈጥፍጠው ጉልበታቸው ነግሎ፣ በወገብ ህመም በጣር ተይዞ ከተኛበት አልጋው ላይ ታዝሎ፣ በትወና መሀል የእግር አውራ ጣት ጥፍሯ ተነቅሎ ወዘተርፈ... ተመልካች ሳያውቅ ደማቸውን እያዘሩ፣ በላብ እየተነከሩ፣ በደም እየሰከሩ ሰርተው ጨርሰው የተዘረሩ ነበሩና፤ አሉምና፤ የጉንፋን ንጥሻ ስለት ሆኖ የሚቆራርጥ ቢሆን እንኳ፤ ለመደናገጥ እጅ መስጠትም ሆነ ለመቆጣትና ይቅርታ ለመጠያየቅ አሁን ጊዜ የለም፡፡

ሦስተኛው ደወል ተደውሏል...
ከፎቁ ላይ የሚለቀቀው መብራት መድረኩን በብርሃን ሲያጥለቀልቀው ፤ ሙዚቃው እየቀነሰ እየቀነሰ ሄዶ ይጠፋና በተዋንያኑ እንቅስቃሴ፣ ንግግርና በየመሀሉ ለማጀቢያ ተብለው በሚቀየጡ የድምፅ ግብዐቶች ይተካል፡፡ ተመልካቹ ተመቻችቶ ለማየት ሲቁነጠነጥ ከየተቀመጠበት ወንበሮቹ ጋ ሲተሻሽ የሚፈጠረው መንቋቋትም እንዲሁ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ይጠፋና በጨለማ የተዋጠው አዳራሽ ፀጥ! እረጭ! ይላል፡፡ የተመልካቹ ልብ በተውኔቱ ታሪክ ስለሚጠመድ፤ ከጎኑ የተቀመጠ ወዳጁን እስከመርሳት ደርሶ፤ በሚመደረከው የፈጠራ አለም ኮርቻ ላይ ተፈናጥጦ፣ እንደየትእይንቶቹ መጠነርእይ የየገጸባህሪያቱን ህይወት ተጋርቶ፣ ጭንቀታቸውን ሲጨነቅ፣ ደስታቸውን ሲደሰት፣ ቀልቡ ተሰርቆ በመጠመዱ ኋላ ይደመማል፡፡ ለዚህም ተዋንያኑ፤ በተጠና የመድረክ እንቅስቃሴና ንግግር፣ የታዳሚያቸውን ስሜት ስቅዘው ይዘው እስከ ተውኔቱ መቋጫ ገቢር ትንፋሽ አሳጥተውት ይቆያሉ፡፡ በቀስታ የተከፈተው መጋረጃ፣ በትዕይንት ማዕዱ ግብዣ እንግዶቹን አርክቶ መልሶ በእርጋታ እስኪዘጋ ድረስ፡፡
በትርዒቱ የረካው ታዳሚ አዳራሹን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት፣ እጅ ነስተው በክብር ለመሸኘት ተዋንያኑ በየተራ እየወጡ ሲሰናበቱ፤ ለሦስት ሰአታት ያህል አንደበታቸውን በውበት ገርተው፣ የቃል ጥናታቸውን ከድርጊት እያዋሀዱ፣ ትንፋሻቸውን እንደየስሜቱ አሰባጥረው፣ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጸጉራቸው በምናብ ተነጥቀው በሰፊው መድረክ ላይ እየተወራጩ የተወናኙበትን የውለታቸውን ምላሽ፣ ከሚያከብሩትና ከሚያከብራቸው ተመልካች የአድናቆት ጭብጨባ ተለግሰው፤ የዕለቱ ትርዒት ፍፃሜ ይሆናል፡፡ ይህም አዲሱ ትውልድ ከነባሩ የወረሰው የአበው ባለሞያዎች ትውፊት ነው፡፡ በተከበረው የቴአትር ሞያ ውስጥ የኖረ ኪናዊ ባህል፤ ...ተመልካችን እንደ የጥበብ ምዕመን፤ አዳራሹን እንደ ቤተ መቅደስ፤ መድረክን እንደ የተቀደሰ ፅላት፤ ራስን እንደ የጥበብ ካህን የመቁጠር “አባዜ”!
በየቤተ ተውኔቱ ያለው የየዕለቱ የትርዒት ውሎም ይህንኑ ይመስላል፡፡ በመሀላቸው ልዩነት ቢኖርም ያን ያህል የጎላ አይደለም፡፡ ትርፍና ኪሳራቸውም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይኸውም እፁብ ድንቅ የትርዒት ጊዜ ቆይታና በታዳሚና ባለሞያ መካከል ነግሶ የኖረው የመከባበር ባህል ላለፉት መቶ አመታት ቋሚ ልምድ ሆኖ የዘለቀ ሞያዊ ቅርስ ነው፡፡ ይህንንም ክቡር ‹ፀጋ› ለዘመናት በፅናት ተሸክመው ያቆዩትና ለትውልድ ያወረሱት፤ የጥበብ ማዕዱን ትሩፋት ለመላው ዜጎቻቸውም ለማቋደስ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ከአፅናፍ አፅናፍ ሲኳትኑ የከረሙ መከራ ያነከታቸው ድሀ ባለሞያዎች ነበሩ፡፡ ምንም እንኳ ዕድሜ ዘመናቸውን የገበሩለት መባዘናቸው ከምስጋና ይልቅ መገለልና እንደ አልባሌ መቆጠርን ቢያበረክትላቸውም፡፡ የሞያ ህይወታቸው እስከ ደም መስዋእትነት ያስከፈለ ተስፋ አስቆራጭ መራር ጉዞ ነበር፤ሰዎቹ ለሞያቸው በቆራጥነት የቆሙ አይበገሬ ባይሆኑ ኖሮ፡፡
በሁናቴያቸው ልክ በጦር ምርኮ የወህኒ አጥር እንደተኮደኮዱ ግዞተኞች አንገታቸውን ደፍተው የኖሩ፡፡ ለአንድ የጋራ አላማ እንደ ጉንዳን ሰራዊት በስርአት የተመሙ ትጉኃን፡፡ ለሞያዊ ስኬት ብቻ የተንገላቱ ፍጡሮች፡፡ ዕለት ተዕለት፣ በቀን ብርሃን ብቻም አይደል በሌት መዐልትም ‹ማህሌት ቆሞ እንደማደር› በጋራ ልምምድ ተጠምደው፣ ከቁሳዊ ምኞት አነጣጥሎ፣ በማይዳሰስ የረቂቅ እርካታ ለስላሳ ላባው የሚያባብለው የጥበብ ሀሴት “ያሞኛቸው”፤ የሞያ ፍቅር በኪን ታዛ አስጠልሎ በጋራ አስተሳስሮ የደቆሳቸው ክቡር እምክቡራን፡፡ ግለታቸው ባላተኮሰው ማህበረሰባቸው ዘንድ በተለያዩ የባካናነት ስያሜዎች እየተሰደቡና እየተናቁ፤ በቤተሰቦቻቸው መካከልም እንኳ እንደማይፈለግ ዋጋ ቢስና ከንቱ የቤተሰብ አባል እየታዩ፤ በጋራ ወደፈጠሩት የጥበብ አድማስ እርቀው በምናባዊ አለም ሲዳክሩ፣ ማንኛውም ተራ ዜጋ የሚገባውን የዜግነት ጥቅማ ጥቅም ከማግኘት ባይተዋር ሆነው፤ ለአለባበሳቸው ግድ ሳይኖራቸው፣ የምድራዊ ተድላ እጅግም ሳያሳሳቸው፣ በጎጇቸው የአውደ አመት ክብረ በአል ከማክበር፣ በማህበራዊ ህይወታቸው፤ ከወዳጅ ጎረቤት ሰርግና ተዝካር ከመካፈል (ለቅርብ ዘመድ ልቅሶና ለቤተሰብ አባልም ሞት ሀዘን) ጊዜያቸውን በጥበብ ውሎ ተነጥቀው፤ የግል ማህደራቸው ሳያሳስባቸው፣ ቤት መስሪያ ቦታ ሳይመሩ፣ የባንክ ቁጠባ ደብተር ሳያወጡ፣ በጨረታና የገበያ ስፍራ ደጃፍ ሳያልፉ፣ በኑሮ የሚደገፉት ምናምኒት ውርስ ቅርስም ሆነ ለህይወታቸው መተማመኛ ኢንሹራንስ ሳይኖራቸው... በእውነት በጣም ያልተለመደ አይነት “ልክፍት” ተጣብቷቸው የኖሩ፤ ግና ታታሪ ስብዕናን ያዳበሩ ምስኪን ባለሞያዎች ነበሩ፡፡ ለአላማቸው የቀኑ፡፡ ለራሳቸው የተከበሩ፡፡ ለእውነታቸው የታመኑ፡፡ በጥበብ የቆረቡ፡፡ እናም በፍፁም ልባቸው የሚያምኑት፤ ነጋ ጠባ የሚያስቡ የሚያሰላስሉትም ነገር ቢኖር፤ እነርሱ የሚያከናውኑት ተግባር እጅግ አስቸጋሪውንና በጣምም አስደሳቹን፣ ለሰው ልጆች እውነት አብሳሪ፣ ወጋገን አብሪ፣ ሀሴት ፈጣሪ የሆነውን ክቡሩን የቴአትር ሞያ መሆኑን ነው። ይኼንን ያህል በስጋም በነፍስም የነሆለሉለት ሞያዊ ፋይዳም ሌላ አይደለም፤አቅላቸውን አጥተው የሚከንፉለት መድረክንና በፍቅር የሚንሰፈሰፍላቸው ውድ ተመልካቻቸውን ማክበራቸው እንጂ፡፡
“ወደ ቴአትር ቤት ሞያችንን አክብሮ ለሚመጣው የተከበረው ተመልካቻችን አጥንትና ደማችንን ለግሰን፣ ህይወታችንን ሰውተን እርካታ ልንሰጠው ይገባል፡፡ የተፈጠርነውም፤ የምንኖርለትም አንድና አንዱ ነገር ይኸው ብቻ በመሆኑ (ሌላስ ምን ሊኖር ይችላል? ቢኖርምኳ ሌላ ጊዜ! አይነት ነገር ነው) መቸስ ሌላ ቀጠሮ/ገጠመኝ አይገጥምም ባይባልም ቅሉ፤ ከዋናው የህይወታችን፤ የህልውናችን፤ የእኛነታችን መገለጫ ጉዳይ፤ ከትርዒት (“ማህሌት” ከመቆም) ሊብስ አይገባውም፡፡ እናስ? እናማ... መድረክ የተውኔት ማዕዱን ተራቁቶ ጦሙን ውሎ አያድርም! ታዳሚ “ምዕመኑም” የሀሴት ቡራኬውን ተነፍጎ አይሳቀቅም! ስለዚህም፤ “ቅዳሴ እንደማይታጎል” ሁሉ፤ ትርዒት አይቋረጥም!”... ነው/ነበር የእምነት ማተባቸው፡፡ The show must go on!
የንሻጤ ምንጭ - GREAT ESSAYS From 16th Century to Present.

Published in ጥበብ

የቀድሞ ስራዎቹን የያዘ አልበም ይወጣል
“አንዲት ሙዚቃ ከጭንቅላቴ ብትወስዱ እንጣላለን”
-አሊ ቢራ /ለአንጎል ቀዶ ህክምና ሀኪሞቹ የተናገረው/

በአንጎል የቀዶ ህክምና ከህመሙ ያገገመው አንጋፋው የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ አሊ ቢራ፤ ሙዚቃ የጀመረበት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በቅርቡ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በሚዘጋጁ የሙዚቃ ኮንሰርቶችና የተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ይከበራል፡፡
የወርቅ ኢዬቤልዩ አከባበሩን በተመለከተ ባለፈው ሃሙስ በካፒታል ሆቴል በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የፕራክሲስ ሚዲያና ፕሮሞሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ቻላቸው “አርቲስት አሊ ቢራ፤ ለአገራችንና ለሙዚቃው ዓለም ትልቅ ስጦታ ነው። የአርቲስቱ ህይወት፣ ስራዎቹና ያስመዘገባቸው ውጤቶች የታሪካችንና የትውፊታችን ጉልህ አካል ስለሆኑ ሊከበሩ፣ ሊዘከሩና ሊጠበቁ ይገባል” ብለዋል፡፡
አሊ ቢራ በ50 ዓመታት የሙያ ጉዞው ላስመዘገባቸው ስኬቶች ዋነኛው መሰረት የህዝቡ ድጋፍ ነው ያሉት አቶ ዘላለም፤በአሉን ማክበር ያስፈለገውም አርቲስቱ ለተዋለለት ውለታ ምስጋናውን የሚያቀርብበትና ደስታውን ከሌሎች ጋር የሚቋደስበት መድረክ ለመፍጠር በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይህ አከባበር አርቲስቱ እምነቱን፣ ዕውቀቱን፣ ዕቅዱን፣ ተስፋውን፣ ራዕዩን በተለያዩ መድረኮች ለሌሎች በማካፈል እስከ ዛሬ ይዞት የመጣውን ችቦ ለሌሎች የሚያስተላልፍበት መድረክም እንደሆነና አርቲስቱ በቀጣይነት ሊሰራቸው ላሰባቸው ሥራዎች መሰረት የሚጥልበት ነው እንደሚሆንም ገልፀዋል፡፡
የ50ኛ ዓመት በዓሉን አስመልክቶ የአሊ ቢራን የሕይወትና የሙያ ጉዞ የሚያሳዩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች እንዲሁም የተሸለማቸው ሽልማቶች የተካተቱበት ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባና በአዳማ እንደሚቀርብና የአሊ ቢራ የተመረጡ 10 ዘፈኖችን በማሳተም ለህዝብ ለማድረስ መዘጋጀቱንም አከባበሩን የሚያስተባብረው የፕራክሲስ ሚዲያና ፕሮሞሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡
ጤንነትህ እንዴት ነው?
ከእግር ጥፍሬ እስከ ፀጉሬ ድረስ ጤነኛ ነኝ፤ ፀጉር ባይኖረኝም፡፡ ማኒጆማ የሚባል በሽታ ነበረብኝ፤ እሱን ለመታከም ጭንቅላቴን ሲመረምሩ እጢ አለብህ አሉኝ፤ እጢውን ካላወጣሁት ደግሞ አይኔ ጠፍቶ ወደ ላይ ቤት እንደምሄድ ተነገረኝ። በዚህ ጊዜ ለማስወጣት ተስማማሁኝ፡፡ ለቀዶ ህክምናውፈርም ስባል “መፈረሙን እፈርማለሁ፤ ነገር ግን ከእጢው ውጪ አንዲት ሙዚቃ ከጭንቅላቴ ውስጥ ብትወስዱ እንጣላለን” አልኳቸው፡፡
የበጎ አድራጎት ስራህ ምን ደረሰ?
ከ50 ዓመት የሙዚቃ ሙያ በኋላ ጡረታ ለመውጣት እያሰብኩ ነበር፡፡ ከሙዚቃው አለም ከወጣሁ በኋላ ደግሞ በአማካሪነት እንጂ የሙዚቃ ስራ አልሰራም፡፡ ስለዚህ ሌላ ስራ መስራት እንዳለብኝ አስብ ነበር፡፡ እኔና ባለቤቴ (ቢሊ ማርቆስ ቢራ) አባቴ ታሞ ወደ ትውልድ ቀዬ ለመጠየቅ ስንሄድ (ባለቤቴ ስራዋ የልጆች አስተማሪ በመሆኑም የተነሳ) ባየነው ነገር አዘነችና “እነዚህን ልጆች መርዳት አለብን” ስትል “እኔስ የምፈልገው ይሄንን አይደለም እንዴ!” አልኩና “ቢራ ቺልድረን ኢጁኬሽን ፈንድ” የሚል በጐ አድራጐት አቋቋምን፡፡ ዓላማው ወላጅ ወይም ቤተሰብ የሌላቸውን ህፃናት መርዳት ነው፡፡ ከድሬዳዋ አምስት ኪሎ ሜትር በምትርቅ አንዲት ወደ ሃረር መሄጃ ገጠር ከተማ ላይ ያሉ ህፃናትን እንረዳለን፡፡ ስንጀምር 130 ነበሩ፤ ፕሮግራሙን ስናስተዋውቅ ወደ ሁለት መቶ ደረሱ፤ አሁን ሁለት መቶ ሰላሳ ደርሰዋል፡፡ ለእነዚህ ህፃናት የትምህርት ቁሳቁስ፣ ዩኒፎርም እና ምግብ እናቀርባለን፡፡ ቦታው ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ሙቀት አለው ግን ውሃ የለም፤ ስለዚህ ውሃም እናቀርባለን። የመማሪያ ክፍሎቻቸው ደግሞ በሳር የተሰሩና የሚፈርሱ አይነቶች ናቸው፤ ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ለማስተካከል ነው የምንሰራው፡፡ ይህንን ፕሮጀክት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለመስራት እቅድ አለን፡፡
ገንዘብ አያያዝ ላይ እንዴት ነህ? ቤት እና መኪና የለህም ይባላል…
ልክ ነው፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቤትና መኪና አልነበረኝም፡፡ አሁን ናዝሬት ላይ በጣም ትንሽዬ ቤት አለን፡፡ ለእኔና ለባለቤቴ በቂ ናት፡፡ እንግዳ ቢመጣብን አንድ ክፍል አላት፤ ትበቃለች። መኪና ግን የለኝም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለብር ግድ ስለሌለኝ ነው፡፡ እጄ ላይ ብር ካለ እስኪያልቅብኝ ድረስ ለሌለው ሰው እሰጣለሁ፤ ግን ዝም ብዬ ብር የምበትን አባካኝ አይደለሁም፡፡
ኢትዮጵያ ጠቅልለህ መጣህ እንዴ?
ወደዚህ ጠቅልሎ ለመምጣት የጤንነት ችግር አለብኝ፡፡ የምፈልገውን መድሃኒትና የህክምና እንክብካቤ ለማግኘት እዛ ይሻላል፡፡ እዚህ እየሰራሁ ለጤንነቴ ደግሞ አሜሪካ እሄዳለሁ፡፡

Published in ጥበብ

በትውልድ ቀዬው ሆስፒታል ሊሠራ አቅዷል
ከቢዝነስ ጋር የተዋወቁት በአዳማ ከተማ ባሠሩት ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ ነው፡፡ ከዚያም እግሩን ስላመመው አሜሪካ ሄዶ ቀዶ ሕክምና (ኦፕሬሽን) አደረገ፡፡ እግሩ በደንብ ድኖ ልምምድ ለመጀመርና ወደ ሩጫ ለመመለስ ረዥም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ያንን ጊዜ በከንቱ ማባከን አልፈለገም፡፡ ከባለቤቱ ጋር ተመካከሩና ሁለቱም ያገኙትን ገንዘብ አንድ ላይ አድርገው ወደ ቢዝነስ ዓለም ገቡ - አትሌት ገዛኸኝ አበራና አትሌት እልፍነሽ ዓለሙ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ አሮጌ ቤቶች ገዝተው አፍርሰውና አሻሽለው በመሥራት መሸጥ ጀመሩ። ከዚያም አትሌቱ በሲድኒ ኦሎምፒክ በማራቶን አሸንፎ ሲመጣ፣ የደቡብ ክልል መንግሥት በሀዋሳ ከተማ 25ሺህ ካ.ሜ ቦታ ሸልሞት ነበር፡፡ በዚያ ስፍራ ገዛኸኝና እልፍነሽ ሆቴልና ሪዞርት ያካተተ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሠርተው የሙከራ አገልግሎት (Soft opening) ጀምሯል፡፡ በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማም በቢሾፍቱ ሐይቅ ባለ 5 ኮከብ ሪዞርት ሠርተው በቀጣዩ ዓመት ይመረቃል፡፡ በአዲስ አበባም በተለያዩ ቦታዎች የእንግዳ ማረፊያ ሕንፃ እያስገነቡ ሲሆን፣ በጥቁር ውሃም ቦታ ተረክበው ምን መሥራት እንዳለባቸው እያሰቡ መሆኑን ተናግሯል፡፡
አትሌት ገዛኸኝ አበራ፤ ያኔ በአርሲ ክፍለ ሀገር አሁን በአርሲ ዞን ኢቴያ በተባለች የገጠር ከተማ በ1973 ዓ.ም ተወልዶ እዚያው አደገ፡፡ ትምህርቱን የተከታተለው ደግሞ በኢቴያና በሁሩታ ከተሞች ነው፡፡ አትሌቱ ገዛኸኝ ወደ ስፖርት የገባው በራዲዮ በሰማው ዜና ነው፡፡ አንድ ቀን ትንሿን ራዲዮ ክምር ስር አድርገው ከአባቱ ጋር እህል ሲወቁ፤ ራዲዮኗ “በፈረንሳይ በተደረገ የ21 ኪ.ሜ ውድድር እገሌ የተባለ አትሌት 1፡02 በመግባት ስላሸነፈ ተሸለመ” የሚል ዜና ሰማ፡፡ በዚያን ጊዜ እሱ፣ ከመንደሩ 21 ኪ.ሜ ርቃ በምትገኘው ኢቴያ ከተማ ነበር የሚማረው፡፡ ጣቷና ማታ የሚያደርገውን ጉዞ ሲያሰላ አትሌቱ ከተሸለመበት ርቀት በእጥፍ ይበልጣል፡፡ “እኔም አሸንፋለሁ” የሚል ስሜት ስለተፈጠረበት ለአባቱ ነገራቸው፡፡ ይኼ የሆነው በ1987 ዓ.ም ነበር፡፡
እዚያው በመንደሩ ሮጥ ሮጥ በማለት ልምምድ ካደረገ በኋላ፣ አሰላ ከተማ ሄዶ በ12 ኪ.ሜ አገር አቋራጭ (ክሮስ ካንትሪ) ተወዳድሮ አሸነፈ። እዚያው በአሰላ ስታዲየም በ5 ሺህና በ10ሺህ ሜትሮች ተወዳድሮ አሸነፈ፡፡ ይኼኔ በፈረንሳይ በተደረገው የዓለም ዋንጫ ውድድር በ21 ኪ.ሜ ኢትዮጵያን እንዲወክል ተመረጠ፡፡ በዚያ ውድድር ግን አልቀናውም፣ 16ኛ ነበር የወጣው፡፡
ከፈረንሳይ ሲመለስ አዲስ አበባ መኖር ስለጀመረ፣ በሙገር ስፖርት ክለብ ታቀፈ፡፡ በዚያን ጊዜ 17 ዓመቱ ነበር፡፡ በሙገር ስፖርት ክለብ ሲለማመድና ሲወዳደር ቆይቶ፣ በ1993 ዓ.ም በሲድኒ በተዘጋጀው ኦሎምፒክ በማራቶን ተወዳድሮ ሲያሸንፍ 22 ዓመቱ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የኦሎምፒኩ አዘጋጆች “በ22 ዓመቱ ማራቶን ያሸነፈ የመጀመሪያው ወጣት” በማለት አሞካሽተውታል፡፡
አትሌቱ አሁን 34 ዓመቱ ሲሆን ከባለቤቱ ከአትሌት እልፍነሽ ዓለሙ ሁለት ልጆች አፍርቷል፡፡ በአምላክና ያኔት ገዛኸኝ ይባላሉ፡፡ አትሌት እልፍነሽ ሁለተኛ ልጃቸውን ከ6 ወር በፊት ነው የወለደችው።
የቢዝነስ ሰው ጊዜ የለውም፡፡ ገዛኸኝ ሀዋሳ፣ ቢሾፍቱና አዲስ አበባ፣ … ብዙ ሥራዎች ስላሉት እየተዘዋወረ ያሠራል፣ ይከታተላል፡፡ ስለዚህ ሥራ ይበዛበታል-ቢዚ ነው ማለት ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ለሥራ ሀዋሳ ሄጄ ነበር፡፡ እዚህ ከደረስኩ ለምን ሆቴሉን አላይም ብዬ ወደ ሆቴሉ ሄድኩ። አጋጣሚ ሆኖ አትሌት ገዛኸኝ ሀዋሳ ነበር፡፡ ሥራ አስኪያጁ ደውሎ ከ“አዲስ አድማስ” የመጣ ጋዜጠኛ እንደሚፈልገው ነገረው፡፡ እሱም፣ ከከተማ ውጭ መሆኑን ጠቅሶ “በ20 ደቂቃ ውስጥ ስለምደርስ ይጠብቀኝ” የሚል መልዕክት አስተላለፈ፡፡ እኔም እሱ እስኪደርስ ድረስ ግቢውንና ክፍሎቹን እየተዘዋወርኩ ስጐበኝ ቆየሁ፡፡
ሥራው አልቆ አገልግሎት የጀመረው የሀዋሳው ባለ 5 ኮከብ ሆቴልና ሪዞርት ስለሆነ እሱን ላስቃኛችሁ። ሆቴሉ የተሠራው ከሀዋሳ ከተማ ዳር ነው፡፡ ከሀዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ፊት ለፊት፣ ወደ ይርጋዓለም፣ ዲላ፣ ሞያሌ፣ … ከተሞች በሚወስደው አውራ ጎዳና ቀኝ ጠርዝ ነው፡፡ ወደ ሆቴሉ ሲታጠፉ የባለቤቶቹ ስም የተጻፈበት እብነበረድ አለ፡፡ ከዚያ ጥቂት ሜትሮች እንደተራመዱ፣ የሆቴሉን ትልቅ ባለ ቅስት መግቢያ ያገኛሉ፡፡ በሩ ሰፊ በመሆኑ፣ ወደ ሆቴሉ የሚገቡና የሚወጡ መኪኖች መተላለፊያቸው የተለያየ ነው፡፡
ግቢው በጣም ሰፊ ሲሆን፣ አረንጓዴ ሳር፣ በየስፍራው የተተከሉ በርከት ያሉ ዛፎችና አበቦች ሲያዩ ሆቴል ሳይሆን ዘመናዊ መናፈሻ ውስጥ የገቡ ይመስልዎታል፡፡ መግቢያውን እንዳለፉ በስተግራ፣ ግራውንድ ቴኒስ መጫወቻ፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ እንግዳ መቀበያውን፣ አዳራሽ እንዲሁም ትንሽ ራቅ ብሎ ባርና ሬስቶራንቱን ያገኛሉ፡፡ ከዚያ ፊት ለፊት ራቅ ብሎ የመዋኛ ገንዳው ይታያል፡፡
እስካሁን ክፍሎቹን አላየሁም፡፡ በባርና ሬስቶራንቱ ጐን፣ ሰፊ ስፍራ አለ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የተሠራው የአስተዳደርና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ሕንፃ ነው። መኝታ ክፍሎቹን የሚያገኙት ከዚያ ሕንፃ ጀርባና ጐን ነው፡፡ ሕንፃዎቹ ሁሉ የጐጆ ቤት ቅርፅ አላቸው። በመጀመሪያው ምዕራፍ የተሠሩት 32ቱ ክፍሎች ፎቅ የላቸውም፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ የሚሠሩት 75 ክፍሎች ፎቅ ሲኖራቸው፣ ግንባታቸው ተጀምሮ መሠረቱ መውጣቱን ባለሀብቱ ተናግሯል፡፡
ገዛኸኝ፣ በሀዋሳ ከተማ የተሠራው ሆቴልና ሪዞርት፣ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሊኖረው የሚገባውን ፋሲሊቲ አሟልቶ በኢትዮጵያ የተሠራ የመጀመሪያው ሆቴል እንደሆነ ይናገራል፡፡ ክፍሎቹ በአራት ደረጃ የተከፈሉ ሲሆን ባለ አንድ፣ ባለ ሁለት አልጋ፣ ትዊንና ልዩ የቤተሰብ መቆያ ኤግስኩቲቭ ቪላ (ባንጋሎ) ናቸው፡፡ ቪላው ራሱን የቻለ የታጠረ ግቢ ሲኖረው፣ የደህንነት ጥበቃውም ልዩ ነው፡፡ ምግብ ማዘጋጃ ኪችን መመገቢያ ጠረጴዛ፣ የወላጆችና የልጆች መኝታ ክፍል፣ እሳት ማንደጃ፣ ግቢው ውስጥ ደግሞ መኪና ማቆሚያ፣ ካምፋየር ማዘጋጃ ስፍራ፣ የጓሮ ፍራፍሬ፣ ማንጐ፣ ፓፓያ፣ አቡካዶ፣ … አለው፡፡ እዚያ ያረፉ እንግዶች ፍሬዎቹን ቀጥፈው መብላትና መጭመቅ እንደሚችሉ ገዛኸኝ ገልጿል። ኪችኑ፣ በተሟላ ምግብ ማዘጋጃ ዕቃዎች የተሟላ ነው፡፡
የልጆች ክፍል፤ ሁለት አልጋ፣ ቁም ሳጥን፣ መታጠቢያ ገንዳ፣ መፀዳጃ፣ ሆቴል ቲቪ፣ … አለው። የወላጆች ክፍል ደግሞ ማስተር ቤድ፣ መታጠቢያ ገንዳና ጃኩዚ፣ ሆቴል ቲቪ፣ ስልክ፣ መፀዳጃ፣ ቁምሳጥን፣ የመልበሻ ጠረጴዛ፣ … ይዟል፡፡ ሳሎኑ፤ ቲቪ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ ፍሪጅ፣ ስልክ፣ የምግብ ጠረጴዛ፣ … በአጠቃላይ አንድ ዘመናዊ ቪላ ሊኖሩት የሚገባውን ነገሮች አሟልቶ ይዟል፡፡ ክፍያው ታዲያ የተጋነነ አይደለም፡፡ አሁን ያለው ሆቴሉ በይፋ ተመርቆ እስኪከፈት ድረስ ጊዜያዊ ዋጋ ቢሆንም፣ በሥራ (በአዘቦት) ቀናት 79 ዶላር ወይም 1,469 ብር፣ ቅዳሜና እሁድ 99 ዶላር ወይም 1,841 ብር ነው፡፡
የክፍሎቹን ብዛት ያየን እንደሆነ 5 ትዊንስ፣ 15 ሲንግል፣ 10 ደብልና 2 ቪላ ናቸው፡፡ ሲንግሉ፣ ቀዝቃዛ ሻወር አለው፡፡ ደብሉ ጃኩዚ፣ ትዊኑ በረንዳ ላይ ዐረቢያን መጅሊስ አላቸው፡፡ ቲቪ፣ ስልክ፣ ሚኒባር፣ ካዝና፣ በሆቴሉ ስም የተሠሩ የተለያየ መጠን ያላቸው ፎጣዎች፣ ሳሙና፣ የፀጉር ሻምፑ፣ ሎሽን፣ የጥርስ ብሩሽና ሳሙና፣ ፀጉር ማድረቂያ፣ መፀዳጃ ቤት፣ ቁም ሳጥን፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ ሶፋ፣ … በሁሉም ደረጃ ባሉ ክፍሎች የሚገኙ ናቸው፡፡
አልጋ የያዙ እንግዶች በተጓዳኝ የሚያገኟቸው ጥቅሞችም አሉ፡፡ ጂም የፀጉርና የጥፍር ውበት (ስፓ)፣ ስቲምና ሳውና ባዝ፣ ዋና፣ ከረንቦላ፣ ግራውንድ ቴኒስና ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቁርስ፣ .. ለሁሉም በነፃ ይሰጣል፡፡
ሆቴሉ የተሠራው ከውጭ በመጡ ዕቃዎች ሳይሆን ግቢው ውስጥ ባሉ ወርክሾፖች በተመረቱ ዕቃዎች ነው፡፡ “የራሳችን የእንጨት፣ የብረታ ብረት፣ የኮንስትራክሽን፣ ወርክሾፖች አሉን፡፡ የሚያማምሩ ዲዛይን ያላቸው ሞልዶች ከውጭ አስመጥተን ግቢ ውስጥ ያነጠፍናቸውና ለጣራ ክዳን የተጠቀምንባቸው ታይልሶች እዚሁ የተመረቱ ናቸው፡፡ እነዚህን የኮንስትራክሽን ዕቃዎች እዚህ ማምረታችን፣ የዋጋና የጥራት ልዩነት አለው፡፡ አንድ ብሎኬት ስታመርት፣ አሸዋውን፣ ሲሚንቶውን … በምትፈልገው የጥራት ደረጃ ቀላቅለህ ትሠራለህ፡፡ ከውጭ አገር ለምሳሌ ከቻይና ስታስመጣ፣ የጥራት ደረጃውን ሳታውቅና ሳታይ ትቀበላለህ፡፡ ለሆቴላችን ክፍሎች የገጠምናቸውን መስኮትና መዝጊያ ስታይ እዚህ አገር እንደዚህ ይሠራል ወይ? ብለህ በጣም ትገረማለህ። ጥራታቸው ከውጭ ከሚመጡት ስለሚበልጥ እዚህ ግቢ ተመረቱ ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡ እነዚህን ነገሮች ለሆቴላችን ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት፣ ለአገራችንም ገበያ ቢቀርብ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ” በማለት በወርክሾፑ ስለሚመረቱት ቁሶች ጠቃሚነት ገልጿል፡፡
መዋኛው ትልቅ እንደሆነ አትሌት ገዛኸኝ ይናገራል። የራሱ ጃኩዚ ሲኖረው፣ 26 ሜትር ቁመትና ከ20.55 እስከ 85 ሜ. ጥልቀት አለው፡፡ “የሕፃናት መዋኛው ጥልቀት 90 ሳ.ሜ ስለሆነ ማንኛውም ሕፃን እንደ ልቡ መጫወት ይችላል” ትላለች፤ የገንዳው ሕይወት አድን ሠራተኛ፡፡ በማከልም፣ “ውሃው ያለውን ኬሚካል በፒኤች ለክተን፣ ክሎሪን ወይም አሲድ እንደጐደለው አውቀን የጐደለውን እንጨምርበታለን። ኬሚካል ስንጨምርበት ከስር ዝቃጭ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ጊዜ ቆሻሻውን በቫክዩም ስበን በማስወጣት እናፀዳለን” ብላለች፡፡
ውሃውን እያጣራ የሚመልስ (ሰርኩሌት የሚያደርግ) መሳሪያ ያለው ሲሆን እንግዶች ዋና ሲደክማቸው ወደ ዳር ተጠግተው፣ ውሃው ውስጥ ባለ መቀመጫ ላይ አረፍ በማለት የተለያዩ ለስላሳ መጠጦችና ፋስት ፉድ የሚስተናገዱበት ስዊሚንግ ባር አለ፡፡
ገዛኸኝ፣ ለሆቴሉ ግንባታ እስካሁን 200 ሚሊዮን ብር መውጣቱንና ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ ካፒታሉ በእጥፍ እንዲጨመረ ጠቅሶ ለ120 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል፡፡ “ከመንግሥት ዋነኛ እቅዶች አንዱ የሥራ አጡን ቁጥር መቀነስ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ፣ ከ250 እስከ 300 ለሚደርሱ በክልሉ ያሉ ዜጐች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ እኔም ትንሽም ቢሆንም በመንግሥት ዕቅድ ተሳትፌ የበኩሌን ድርሻ በማበርከቴ ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡
አትሌቱ በማኅበራዊ ተሳትፎም አይታማም፡፡ በግል ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ፣ ከመንግሥት ጋር በመሆን፣ በተወለደበት አከባቢ ጥሩ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ይናገራል፡፡ “የአካባቢው ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ምንድነው የሚያስፈልገው? ት/ቤት፣ ሆስፒታል፣ ውሃ፣ … በማለት ባደረኩት ጥናት፣ የሕዝቡን ፍላጐት (ፊድ ባክ) አግኝቻለሁ፡፡ በተወለድኩበት አካባቢ ሆስፒታል የለም፡፡ ሕዝቡ፤ ከኢተያና ከሁሩታ አካባቢ አሰላና አዳማ እየሄድ ነው የሚታከመው፡፡ አካባቢው ሰፊና ሕዝቡም ብዙ ነው። በዚያ አካባቢ ሆስፒታል ለመሥራት አቅጃለሁ፡፡ አሜሪካ፣ ፊንላንድና ጀርመን እግሬን ኦፕሬሽን ካደረጉ ሐኪሞችና ሰዎች ጋር መሳሪያዎችን በዕርዳታም ሆነ በሌላ መንገድ ለማስገባት ተነጋግሬ ጥሩ ምላሽ አግኝቻለሁ፡፡ ስለዚህ፣ ሕዝቡ በአነስተኛ ክፍያ ሊጠቀምበት የሚችል ሆስፒታል ለመገንባት እያሰብኩ ነው፡፡ በቅርቡም መሬት እረከባለሁ የሚል ሐሳብ አለኝ” ብሏል፡፡
በሐሳብ ደረጃ ይሁን እንጂ በተወለደበት አካባቢ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ያሰባቸው መስኮች እንዳሉ ገልጿል፡፡

Saturday, 26 October 2013 14:06

ያላለቀው ዳንቴል

…በበሬ ክፍተት የገባው የጠዋቱ ብርሃን ስለታም ሰይፉን ወድሮ ከወለሌ ላይ እንደጠገበ ጐረምሣ ተገትሯል፡፡
“ውጪ ውጪ” የሚለው ስሜቴን መግረዝ አልቻልኩም!…በደረቴ ተኝቼ የማነበው የአረጋሽ “ያላለቀው ዳንቴል” መጽሐፍ መስጦኛል…፤ ግን በመሀል ይሔ ሐሳብ እንዴት ሊመጣብኝ ቻለ…? አሃ…ይሔ ፍርድ አወቅ ነዋ” መጽሐፉ ውስጥ ያለው አንኳር ገጸባህሪ ነው፡፡ “ዛሬ እጮኛዬ ነሽ…ነገ ደግሞ ሚስቴ” ያላትን በዚህ በሰንበት እረፍቷን አወጀላት (የልቡ ካላንደር ላይ) ቤቱ ውስጥ ጉድ ጉድ እያለ ነው፤ እሷማ እሷ ናት…
የጡት ማስያዣዋን እና ሙታንታዋን ሲያጥብላት…የሆነ የቅናት መንፈስ ውስጤን ሰቀዘው፤ አናወጠችኝ፡፡ እሷ ደግሞ እንዲህ ሲሆን ግማሽ ሴትነቷን የተጋራት እየመሰላት አስታዋሽ እንዳጣ ወተት አልጋው ላይ ተጥዳ ተበጣጥሳለች! አትወደውም…ግን ደግሞ ትወደዋለች…”ንጉሤ” ትለዋለች፤ አልጋ ላይ ሲሆኑ፡፡ ዳንቴልነቷን ይተረትርላትና እንደገና…
“እንደዚህ በላይሽ ላይ ወፍ አትብረር የምለው…ቅናት እንዳይመስልሽ…እረፍትን እንድታጣጥሚልኝ ስለምፈልግ እንጂ…እንደ ድሮ ወንዶች ከስራ ብር ብለሽ መጥተሽ…እቤት ውስጥ ተንደፋድፈሽ ሆዴን እንድትሞይልኝ…የሥጋ ሥሜቴን እንድታረኪልኝ ጠልቼ አይደለም…በሥራ እየባተልሽ ድስትሽ ሲገነፍል…
“ማነሽ ድስቱ ገነፈለ ማለት ቀላል ነው…” ቲቪ ውስጥ ሆኖ የሚተውን ተዋናይ መሠላት…የሌባ ጣቷን ወደፊቱ ቀስራ …“ና” አለችው፣ እሱም መደስኮሩን ትቶ እንደታጠቀ ወታደር በተጠንቀቅ ሄደላት፡፡
“እዚህ ላይ ጥብቅ አድርገህ ሳመኝ?” ያተኩሳል። ከተባለው ቦታ ሌላ አንገቷ ስር ሳማት… አይኗን ጨፍና ትስለመለማለች፡፡
ወደ ደረቷ እየተንሸራተተ …ይቃኛታል፤ ክራሩ በአግባቡ “ትዝታን” ይደረድራል፡፡
ሁለቱም እኩል ያዜማሉ፡፡ ከት ብለው እንደመሳቅም አይነት፡፡ ደስ የሚል ሳቅ… ከተራራ ላይ እንደነጋሪት ሲጐሰም የሚሰማ፡፡ ለምን ሳቅ ከነጋሪት ጋር ተገናኘ የሚለኝ ካለ መብቴ ነው! እንደውም አፄ ምኒልክ አድዋ ይዘውት የዘመቱትን ሰራዊት ይመስላል…አተማመሙ፡፡ እና እንደ አብሪ ጥይት በጥቀርሻ ሰማይ ላይ “ጢው” ብሎ እንደሚጠፋው ማለት አለብኝ?…
በሰፊው መሬት ላይ አንድም ወጣ ገባ በሌለው፣ ደረቱን ለሰማይ አስጥቶ እንደጐረምሳ ደረት በፀጉር እንደታጀበው፣ መሬቱም በለምለም…የሳቀ ሳር አጊጧል፤ የመሬቱን ውበት በለስላሳ ጣቷ ገብታ ሳሩ ውስጥ የምታርመሰምሰዋ ፀሐይ፣ አበሻ ቀሚሷን በጥለት ባጌጠ የሳቅ መቀነት ሸብ አድርጋ ልቧ እስክስታ እየደለቀ ነው፡፡
ወድቆ የነበረው የአክሱም ሐውልት ቆሟል፡፡ የሷም የስሜት ቀስት ተወጥሯል፡፡
እንኳን የአዳም ፍጥረት ቀርቶ ተፈጥሮም ስትስቅ ለብዙ ዘመን ስንቅ ይሆናል፡፡ እንዲህ በንፁህ ልብ ሸራ ላይ ያልሳሉት ሥዕል መልክ አልባ ይሆናል… የክራሩ ድምጽ ቀነሰ …ሳቋ እርካታን እያለከለከለ…ሰማዩ ደረት ላይ ተዘረረ…ሰማይ ደግሞ ሃበሻ ነው፡፡”
ይሔን ገጽ መላልሼ አንብቤዋለሁ፡፡ እቺ አረጋሽ የፍቅር አገላለጿ ተመችቶኛል፡፡ የእርካታው መረብ እኔንም ሳያጠምደኝ አልቀረም፣
ማናት ሰላም ባለው ፍቅር እማትቀና? ማናት ሳቋ እንደማታዋ ፀሐይ ወርቃማ እንዲሆንላት እማትመኝ? ማናት ነፃነቷን እሚያውጅላት ወንድ ማትሻ…? ማናት መብቷን እስከመገንጠል እንዲዜምላት አብራ እማታዜም ርግብ…?
ማናት ለባሏ አባወራ ሆና፣ እማወራ ባል ማታልም…? ይሄ ሁሉ ነፃነት ለነፃነት ቀለም አጊጦ በጠራ ሰማይ ላይ ያለከልካይ ሲስቅ…አቦ የምር ቀናሁባት፣ ፍርድ አወቅን ብነጥቃት…እቺ ከረፈፍ ተሰጥቷት ምላሹን ንፉግ የሆነች…እንዳንቀላፋች በደንብ አስተኝቼ ውዱን የእኔ ባደርገው ተመኘሁ፡፡
ሳስበው…ያጣችውን በሙሉ ሰጥቷታል…ምንም ስለሌላት ለመቀበል አቅሙ አልነበራትም…በባዶ ሜዳ እናቷ እንደሞተችባት ጥጃ ባተለች…
ሸክላ በሸክላ ሠሪው ላይ የማመጽ ምንም መብት የለውም! ሲፈልግ መልሶ መላልሶ…ያቦካካዋል…ጥሩ የአበባ ማስቀመጫን ጀበና በማድረግ፡፡ ”ደከመኝ” ስትለው ከበር ጀምሮ እቅፍ ያደርግና መኝታ ቤት አስገብቶ…ልብሶቿን ቀይሮ፣ እግሯን ለብ ባለ ውሃ አጥቦ…እየኮረኮራት ያስተኛታል…አስቆ፡፡ እሷ ግን ከመተኛቷ በፊት ምንም አይነት ጣዕም ሳታቀምሰው ማንኮራፋቷን ትጀምራለች፡፡ እንዳይበርዳት ግልጽነቱን “በፍቅር ጋቢ ጀቡኖ ያለብሳትና ሥትነሳ ለምትጐርሰው ይሯሯጣል፡፡” እና ፍርድ አወቅን ብወደው አይደለም ባፈቅረው ቅር የሚሰኝ አለ…?
“ወድቃ የተገኘች ልጅ ናት… ምስኪን መሀን አሮጊት …ከገንዳ ውስጥ አውጥተውኝ ከጉንዳን ቀምተው ማድቤት ውስጥ አመድ ልሰው አሳደጓት፡፡
ፍርድ አወቅ ያገኛት…ጨርቅ እና እንትኗን የቀደደችለት ጐረምሣ…ሠርክ እየሰከረ እንትኗን የቀደደበት የጌሾ ጫካ ውስጥ ያለ ርህራሄ እንትን ካረጋት በኋላ…አይንሽን ለጌሾ ብሏት የጠፋ ጊዜ ነበር፤ ያውቀዋል ጐረምሣውን…እሷንም ጠንቅቆ። ታዲያ ለምን ውሃ ላኝክ? አጥሚት ልቆርጥም ያሰኛታል?”
ተመልሼ መቶ አስራ አንደኛው ገጽ ላይ ያነበብኩት ነው፡፡ እቺን እርጥብ ነው የወደደው…
“የህሊናዬን ለውጥ የማየው ውስጤን ሳፀዳው ነው፡፡ አሁን የገባኝ መንፃት፣ ዓይኔ ላይ የተጋረደው ሩቅ አለመመልከት…ማንም የለጠፈብኝ አይደለም፤ እኔ መግፈፍ ስላልቻልኩ እንጂ እኔ ውስጥ እነዛ የወለዱኝ ነበሩ…እነሱ ሳያንሱ ራሴን ጠልፎ ለመጣል እሮጥ ነበር…ይመጣል ብዬ ስጠብቅ አልሄድኩምና ቀረ…”
ተስገብግቤ የመጨረሻውን ምዕራፍ ሳነበው ነበር የዋህነቷን ሞኝነቷ ጠልፎ እንደጣለባት ያወቅሁት፡፡ የሆነ ተስፋ ተሰማኝ … ፍርድ አወቅን ፈልጐ ለማግኘት…ያወቅሁትን እንዳላወቅሁ አስቤ ተመለስኩ ወደ ንባቤ…
“የሰማዩ ስፋት የሚታይህ ባጠበብከው የአይንህ መጠን ነው…አዕምሮህም ርቆ የሚሄደው አንተ በለካኸው ተበጣሽ ክር እንጂ በብርሃን ልኬትህ መጠን አይደለም፤ አርዝመን ካሰብን ሰፊ መሰብሰብ እንችላለን… ራሳችንን ለመደሰት ካላዘጋጀነው ጉልበታችንን አቅፈን ቁጭት እናዜማለን፣ ፍርድ አወቅ እንደዛ አይደለም፣
እስክስታ እሚመታ ሳቅ ካማረህ በፍርድ አወቅ የዋህነት መጠለል ይኖርብሃል፤ ለእውነተኛ ፍቅር ተንበርክኮ መገዛት ካሰኘህ ፍርድ አወቅን መሲህ አድርገው፤ ፍርድ አወቅ ሲወድ የምሩን ነው፡፡ ሲሰጥ አይሰስትም፡፡
ሲስቅ ህዝባቸው ላይ ቂም የፀነሱ መንግስታት ካዩት ይቅርታ ይጠይቃሉ፤ የበደሉትን ህዝብ፡፡ ፍቅር ሲሰራ…ስልጣን ላይ ችክ ያለን ገዢ ያላንዳች ማንገራገር
“በቃኝ”ን ያስመኛል፡፡ ፈጣሪውን ሲያመሰግን ቢሰሙት በዘር፣ በሀይማኖት፣ በመሬት … መሻኮት ከንቱነት መሆኑን ይረዳሉ…ብቻ ፍርድ አወቅ ጋ ሳቅ…በጥለት ያጌጠ የሀገር ልብስ ነው፡፡”
እቺ አረጋሽ እንዴት አባቷ ነው እምትገልፀው! እርግጠኛ ነኝ ፍርድ አወቅ ላይ ፎንቃ ገብቶላታል…እናቷንና! እሷ ነሁልላ እኔንም አነሆለለችኝ እኮ…፡፡
“ወድቀሽ ስለተገኘሽ ክብር አይገባሽም አላልኩሽም፣ ሴት ልጅ ፈቅዳና ወዳ ክብሯን ካልጣለች በቀር…አክሊል ናት፤ ግን ሳታውቀው ይሁን አውቃው ምቾት አደናቅፎ ይጥላታል፣…ያኔ እንኳን ራሷን ችላ ለመቆም ቀርቶ ተረባርበው ቢያነሷት እንኳ ፈቅዳ ወድቃለች እና ውዱቅ ናት። ማናችንም ስንወለድ እማናውቀው ሰው እጅ ላይ እንወድቃለን…ከዛ በኋላ ነው…ህይወት ራሷ ብቅልና ጌሾ ሰብስባ…” ጌሾ ሲል ልቧ በረገገች…እፍ የተባለ ገለባ ይመስል…አይኖቿ እየጠበቡ መጡ…ሀይል እንዳጠረው አምፖል፡፡
“እሚጥምም … እሚጐመዝዝም ‘ህይወት’ የምትጠነስሰው፡፡ በመንገዳችን ላይ ራሳችን ደንቃራ እንሆናለን … ለራሳችን …” እሱ የመኝታ ቤቱ ምንጣፍ ላይ ዝርፍጥ ብሎ ተቀምጦ … እሷ ያማረ የአልጋ ልብስ በከፊል ደርባ አልጋው ላይ ናት … እንዲህ ቁም ነገር እያወራ ተኛች … እያንኮራፋች …፣ እንዲበርዳት አልፈለገም … የተለመደ ደግነቱን አልነፈጋትም። አልብሷት ትራሱን አመቻችቶ …ወጣ፣… ሥትነሣ እምትቀምሠው ለመሥራት፡፡”
አሁን ሙሉ በሙሉ ቤቴን ጐረምሳው ብርሃን ተቆጣጠረው … ለረጅም ሠዓት በደረቴ ስለተኛሁ ነው መሠለኝ ጡቶቼን የህመም ሥሜት ተሠማኝ … “ውጪ! ውጪ!” የሚለኝ ስሜት በመጠኑም ቢሆን ትዕግሥት ያገኘ ይመስላል … “ያላለቀው ዳንቴል”ን ይዤ ተነሳሁና የቤቴን መስኮት ከፈትኩ … ነፋስ ጐበኘኝ … ጐረምሣው ‘እፎይ’ ብሎ ተደላደለ። እኔም ውስጤን የሆነ ነገር ተሠማኝ … ‘ውጪና አግኚው…’ ደግሞ ቁርስ መብላት አማረኝ፤ የቀረኝን … ተስገብግቤ መጨረሻውን ባነበውም … ትንሽ ገፅ ነው …፣ ማቋረጥ ፍርድ አወቅን መበደል መሠለኝ … ያቺ ከረፈፍ እማ ወየውላት …!
ተመለስኩ … በልቤ እየሳቅሁና እያፏጨሁ … ወደ ንባቤ … ትራሴን አመቻችቼ ካቆምኩበት ቀጠልኩ … የጣፈጠኝን አገላለፅ ደጋግሜ አጣጥሜዋለሁ፡፡
“ቢያንስ ያዘዝኩሽን ደስተኛ ሆነሽ መፈፀም ነበረብሽ …”
“ረሳሁት!” ትዕቢት ልቧን ነፍቷታል፡፡ በጭቃ አለም እሚረገጥ ድንጋይ ሲገኝ ማን ያላቁጣል!
“እንዴት ሰው ለራሱ የራሱን ጉዳይ ይረሳል…?” በዓይኑ እውነት ረጨላት፡፡
“ውይ ፍርድ አወቅ አትጨቅጭቀኝ!... ለምን መጣሽ ከሆነ እሄድልሃለሁ…” አተኩሮ ተመለከታት … ሔዳስ …? የት ነው ማረፍያዋ? … ዛፉ እሱ ብቻ ነበር … የትም አትሔድም ብሎ አልነበረም የወደዳት … ከልቡ ጥላ ያስጠለላት፡፡ ለራሷ ብሎ ነበር፡፡
“የቀረብሽ አንቺው ነሽ …” እየተመናቀረች ወደ መኝታ ቤት ገባች … ጫማዋን ሳታወልቅ … እግሯ መሬት እንዳለ በጀርባዋ ተጋደመች … ቀስ ብሎ ተከትሎ ሲቃኛት … ፊቷን በከፊል በሻርፕ ሸፍና ተደብቃለች … ከማን? ከህሊና…? ወይስ ካፈጠጠባት እውነት …? ተመልሶ ለብ ያለ ውሃ ይዞ መጣ … እግሯን ካጠባት በኋላ በፎጣ እያደራረቀ … እቅፍ አድርጐ በብርሃን መሠላል … እየተረማመደ ቀሚሷን ገፎ ጣለ … ሽቅብ አመራ … ዳገቱ ብዙም አስቸጋሪ አልነበረም … ዋናው የተራራው አናት ላይ ሲደርስ ትንፋሹ ይፋጅ ነበር … ዝቅ ሲል … የብርሃኑ መሠላል ከቦታው አልነበረም፡፡
የገዛ አንድ ቋሚ መሠላሉን (ካስማ) ዘረጋና የሆነ አቃፊ ሥፍራ ውስጥ በአደራ ዶለው፡፡”
ለምንድነው እንዲህ የሚያቁነጠንጠኝ …? ምናለ ይሔን ሁሉ ነገር ከእኔ ጋር አድርጐት ቢሆን … ሰው ግን ስስታምነቱ ነው እንዴ ቀድሞ የተፈጠረለት…!? ለምንድነው በጥሩ ወንድ እና በጥሩ ምግብ እኛ ሴቶች የምንቋምጠው? … ልጅቷ የምር እያበገነችኝ ነው፡፡ እኔ ብሆን መታጠቢያ ቤት ወስጄ ለሰስ ባለ ሙቅ ውኃ አብረን ከታጠብን በኋላ ፍቅር እየዘመርኩለት፣ ሳቅ እንደ አበባ እየበተንኩለት … ቀኝ እጁን እንደ ሙሽራ እየጐተትኩ … መኝታ ቤት ወስጄ … ወይኔ…!
“ሁለቱም ጭድ እንደሌለው የጭቃ ቤት በርጥበት ተፈነጋገሉ … እሱ ግራ እጁን አንተርሷታል … እሷ ጀርባዋን ሰጥታው … ግድግዳው ላይ አፍጥጣለች …” ፈጣጣ…! ምናባቷ ዞራ ጥምጥም አርጋ አታቅፈውም! “ግራ እጁ ላይ ደሙ የረጋ መሠለው … የመደንዘዝ ሥሜት ወረረው…” እኔን ይደንዝዘኝ! “በከፊል የተራቆተ ገላዋን በጥለት ባጌጠ የአልጋ ልብስ ሸፈነላት፡፡ ራቁት ማየት አይወድም… ጀርባዋን ስለሠጠችው ሌላ አላሠበም … እንዳይበርዳትና እንዳትራቆት ተጨንቋል …”
የምር ደም የምታፈላ ሴት ናት! ከየት አባቷ የመጣች ፋራ ናት በጌታ … ቱ…!፡፡ አራት ገፅ ቀርቶኛል … ከአራቱ ግማሹን አውቀዋለሁ … መጨረሻውን እያወቅነው እንዳላወቅን መሆን አይደል ህይወት … ፍርድ አወቅን ማግኘት አማረኝ … አማረኝ ብቻም ሳይሆን ሰውነቴ በሙሉ በመፈለግ ሞረድ ተሞርዶ ስል ሆኗል፡፡ …
***
“የጠበቅሁትን ባላገኝ ግድ አይሠጠኝም … ለራሴ ታማኝ ነኝ…”
“እኔ እኮ በቁንጅናም በስርዓትም እበልጣታለሁ…”
“ያላት ይበቃኛል!”
“ከሷ በላይ እወድኃለሁ!”
“የሷን ያህል አላፈቅርሽም!”
“ወደኸኛል ማለት ነው?”
“ሰው ጠልቼ አላውቅም”
“እኔ ራሴን ችዬ የምኖር ሰው ነኝ፡፡ ለሠጡኝ መመለስ አያቅተኝም …”
“እሷ በእኔ የመፈለግ ከረጢት ውስጥ የታሠረች ውዴ ናት …”
አይን አይኑን እያየሁ ይበልጥ ወደድኩት … ሳላስበው እንባዬ ሊያመልጠኝ ነበር … ታገልኩ … ጥርሴን ነከስኩ … በሠፊው ወደ ውስጤ ትንፋሽ ሳብኩ …
“በጊዜ ስለምትመጣ በር ከፍቼ ልጠብቃት…”
“እኔ ሐሳቤን መች ጨረስኩልህ…?” መለማመጥ እንዳይመስልብኝ ፈርቻለሁ … እርግጥ ሐሳብን መናገር … ፍቅርን መግለፅ … ለትምክህተኞች ካልሆነ በቀር … መለማመጥ አይደለም፡፡
“ልንጠቅህ አልኩ እንዴ…?”
“እኔ አልቆብኛል…!” የሆነ ነገር ከእኔ እየጠበቀ ነው፡፡
“ስሟን አልነገርከኝም…?”
“ልቤ ያውቃታል፡፡” ሳቅሁ … ሙሉነቱ ይመስጣል … እየኮራ እንዳልሆነ አውቃለሁ … ቢኮራም ደግሞ መብቱ ነው!፡፡
“የምሬን ነው … ስሟን አ.ል.ነ.ገ.ር.ከኝ.ም…” ሳይገረም አይቀርም፡፡
“ስምረት”
ምን ማለት ነው…? ለራሴ የጠየኩት ጥያቄ … ምንም የሠመረ ነገር አይታይባትም … መልኳም መልክ የለውም … ፀባይዋም እንደተናቆረ ህዝብና መንግስት ያኮረፈ ነው፡፡ ያስታውቅብኛል … ድብን አድርጌ ቀንቻለሁ፡፡
“ያንቺን አልነገርሽኝም…” አቤት እንዴት ደስ እንዳለኝ …
“ሶስና …” ፊቱ ላይ ደስ የሚል ፈገግታ ተስሏል … እሚያምረው መልኩ፣ ሲስቅ የሚረጨው ብርሃን በቀስታ ደመና የተለጠፈ ነው … ታድሎ … ባነንኩ፣ ቤት ነኝ … “ያላለቀው ዳንቴል”ን አርቄ አስቀምጬዋለሁ …
የምር ፍቅር ይዞኛል… ውድድድድድ አድርጌዋለሁ … እንዲህ እስክነሆልል ድረስ… ዋልጌ የሚለኝ አይጠፋም… ማን በመታመን እና በቅንንት የታሸን ወንድ ይጠላል… ጅል ሴት ካልሆነች በስተቀር እሚወደድን መውደድ ነው፡፡ ማን ጐንበስ ብሎ ቀና የሚያደርግን ያጥላላል…? ማንም! ጥሩውን መጥፎ የምናደርገው ራሳችን ነን፡፡
የእኔ የዘቀጠ አስተሳሰብ ጥሩውን ካዛባ ይለውሰዋል … ወይ መተላለፍ…!
ለምንድን ነው ፍርድ አወቅን የወደድኩት…? ብዙ መሳጭ ታሪክ አለው … ወድቆ ሰው እንዲወድቅ አይጥርም… በጠንካራው ስብዕናዬ… ገርበብ ብሎ በተከፈተው ልቤ ሠተት ብሎ ገብቷል፤ ባፈቀራት ሴት ገላ ውስጥ እኔ ተኛሁለት፡፡
ወይ “ያላለቀው ዳንቴል…”!

Published in ልብ-ወለድ

ዓይኖቻችን በየዕለቱ 15ሺ ያህል ጊዜ ይርገበገባሉ
እያንዳንዱ ሰው በቀን 2 ሊትር ምራቅ ያመርታል
በየደቂቃው ከ30ሺ - 40ሺ የቆዳ ሴሎች ይሞታሉ

ከተፀነስንበት ሴኮንድ ጀምሮ፣ በሕይወትና በጤንነት የምንንቀሳቀሰው ቅንጣት ታህል ስህተት ሳይፈፅሙ ተግባራቸውን ስለሚፈፅሙ ነው፡፡ እስቲ ጥቂቱን እንይ፡፡

20ሺህ ያህል ሀሳቦች
በአንጎላችን ውስጥ ምን ያህል የነርቭ ሴሎች እንዳሉ ያውቃሉ? እጅግ በርካታ ናቸው-እስቲ ይገምቱ፡፡ በአንድ ሴኮንድ ውስጥ በአማካይ ከአምስት እስከ 50 ጊዜ እርስ በርስ መልእክት ይለዋወጣሉ፡፡ የነርቭ ሴሎች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች በቀን ከ10ሺ ኪ.ሜ በላይ ይጓዛሉ፡፡ ከአዲስ አበባ አስመራ ድረስ አምስት ጊዜ እንደመመላለስ ነው፡፡ የነርቭ ሴሎቹ ቁጥር ከመቶ ቢሊዮን በላይ ነው፤ የፀጉር ያህል ውፍረት የላቸውም፡፡ በመሃላቸው ያለው ርቀትም እንደዚያው ኢምንት ነው፡፡ ነገር ግን ከብዛታቸውና በየሴኮንዱ ከሚለዋወጡት የመልእክት ብዛት የተነሳ ተዓምር ይፈጥራሉ፡፡ አንድ ነገር አይተው ወዲያውኑ “ይሄ ውሻ ነው፣ እንዳይነክሰኝ!” “ብርቱካን ነው፣ ይጣፍጣል” “ሰው ነው፤ ዝነኛው ሯጭነቱ ይደነቃል” “አንበሳ ነው፣ የጀግንነት ምሳሌ ተደርጎ ይቆጠራል” … ለማለት የሚችሉት በዚህ ፍጥነት ነው፡፡ በእነዚህ ነርቮች ነው እንግዲህ በቀን፣ 20ሺህ ያህል ጊዜ የምናስበው።
እንደ በረዶ እንዳንቀዘቅዝ፣ እንደ ውሃ እንዳንፈላ
የሰውነታችን “አውቶማቲክ” እንቅስቃሴዎችንና ሂደቶችን የሚቆጣጣረው hypothalamus የተባለው የአንጎል ክፍል ነው፡፡ የሰውነታችን የሙቀትና የቅዝቃዜ መጠን ከልክ እንዳያልፍም ይቆጣጠራል፡፡ በአንዳች ውጫዊ ወይም ውስጣዊ ምክንያት የግማሽ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ለውጥ ከተፈጠረ፤ ሰውነታችን ሕይወት አድን የሙቀት መጠን ማስተካከያ ያከናውናል፡፡
የሰውነታችን ሙቀት በጣም ከፍ ሲል፣ በቆዳችን ውስጥ ያሉ የደም ስሮች ይሰፉና ሙቀት ያስወጣሉ፡፡ ቅዝቃዜ ሲከሰት ደግሞ የደም ስሮች ጠበብ ይላሉ፤ ላብ አመንጪ ዕጢዎችም ይዘጋሉ፡፡ ቅዝቃዜው ሲበረታማ ሰውነታችን ሙቀት ለመፍጠር መንቀጥቀጥ ይጀምራል፡፡

የልብ ምት
የትም ሆነ የት ቢሆኑ፣ ሲራመዱም ሆነ ሲያንቀላፉ፣ ልብ በአንድ ደቂቃ ከ60 እስከ መቶ ጊዜ ይመታል፡፡ በአማካይ ልብዎ በቀን መቶ ሺህ ጊዜ ይመታል፡፡ በዚህ ስሌት ስድሳ ዓመት አማካይ ዕድሜ ላይ የደረሰ ሰው ከ2 ቢሊዮን ጊዜ በላይ የመታ ልብ ይኖረዋል፡፡
በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ የደም ስሮች ብዛትና ርዝመት ጉድ ያሰኛል፡፡ ከጫፍ ጫፍ የተቀጣጠሉ 160 ሺህ ኪ.ሜ ያህል ይረዝማሉ፡፡ የደም ማጣሪያ ባይኖር ኖሮ፣ ሰውነታችን ምን ያህል የደም መጠን እንደሚያስፈልገው ያውቃሉ? በቀን 5,720 ሊትር! በሌላ አነጋገር እንደ ሳንባ፣ ጉበትና ኩላሊት የመሳሰሉ የደም ማጣሪያ የሰውነት ክፍሎች በቀን ወደ 6ሺ ሊትር ገደማ ደም የማጣራት አቅም አላቸው ማለት ነው፡፡

ሳይፈልጉ በቀን 25ሺህ ጊዜ መተንፈስ
አልመውና አቅደው 25ሺህ ያህል ጊዜ ልተንፍስ ካሉ፣ ሌላ ነገር በፍፁም አይሰሩም፤ እንቅልፍም አይተኙም፡፡ ቀንና ሌት ስራዎ መተንፈስ ብቻ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አንጎላችን የመተንፈስ ልምድን አውቶማቲክ ስላደረግልን ምስጋና ይግባው፡፡ ለመሆኑ በየጊዜው አየር ወደ ውስጥ የምንስበውና የምናስወጣው (የምንተነፍሰው) ለምንድነው?
የሰው ልጅ ፍጡራን በእያንዳንዷ ደቂቃ ከ200 እስከ 300 ግራም ገደማ ኦክስጅን ያስፈልገናል፡፡ ይህንን የማያቋርጥ የአየር ፍሰት ለማስተናገድ ሳንባችን ውስጥ 300 ሚሊየን ያህል ለዓይን የማይታዩ alveali የተባሉ የአየር ከረጢቶች ተዘጋጅተው ይጠብቃሉ፡፡ የተቃጠለ አየር (ካርቦንዳይ ኦክሳይድ) ከደማችን ያስወግዳሉ፤ ኦክስጅንን ተቀብለው ለደማችን ያስረክባሉ፡፡

የዓይን ጡንቻዎች
አንድ ነገር ላይ እንድናተኩር የሚረዱን የዓይናችን ጡንቻዎች በቀን 100ሺህ ጊዜ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህም ከ80ኪ.ሜ ጉዞ ጋር እኩል ይሆናል፡፡ ዓይኖቻችን በየእለቱ 15ሺህ ያህል ጊዜ ይርገበገባሉ፡፤ ለምን እንደሆነ ያውቃሉ? ዓይንን ከአደጋ ለመከላከል፣ ቆሻሻ ለማስወገድና ዓይንን ለማርጠብ ነው፡፡ ዓይናችንን ስንጨፍንና ስንከፍት ያመለጠንን መረጃ አንጐላችን ስለሚያሟላልን መጨፈናችን እንኳ በፍፁም ትዝ አይለንም፡፡

ሁለት ሊትር ምራቅ
ሰውነታችን በቀን የሚያመነጨው ምራቅ ከጥቂት ማንኪያ የማይበልጥ ሊመስለን ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ሰው በቀን ሁለት ሊትር ምራቅ ያመርታል፡፡ “አቤት! ምን ሊጠቅም?” ሊሉ ይችላሉ፡፡ ያለ ምራቅ አንድ ነገር መቅመስ፣ ምግብ መዋጥም ሆነ ቃላት መፍጠር አንችልም፡፡ በዚያ ላይ፣ ምራቅ ከፍተኛ የጀርም ጠላትና የምርቀዛ (የኢንፌክሽን) መከላከያ ነው፡፡ ስለዚህ፣ እንስሳት ቁስላቸውን ሲልሱ ማየት አያስደንቅም፡፡

በሴኮንድ 3 ሚሊዮን ቀይ የደም ሴል
በየደቂቃው፣ ከኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር በእጥፍ የሚበልጡ ቀይ የደም ሴሎች በሰውነታችን ውስጥ ይፈጠራሉ፡፡ የዚያኑ ያህልም ይሞታሉ፡፡ በቀን 260 ቢሊዮን ያህል ቀይ የደም ሴሎች እናመርታለን ማለት ነው፡፡ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ኦክስጂን ለሁሉም የሰውነታችን ሴሎች የሚዳረሰው በቀይ የደም ሴሎች ነው፡፡ አንድ ጠብታ ደም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቀይ የደም ሴሎች ሲኖሩት፣ ቀዩን ቀለም የሚያገኙት ሄሞግሎቢን ከተሰኘው ፕሮቲን ነው፡፡

መብላትና መጠጣት ጥበብ ነው
ምግብ መዋጥና ፈሳሽ መጠጣት ቀላል ጥበብ እንዳይመስላችሁ፡፡ ህፃናት ሲቸገሩ ካላየን በቀር በእግር ቆሞ መራመድ ቀላል ይመስለን የለ? ጥበብ ነው፡፡ ምግብ መዋጥና ፈሳሽ መጠጣትም እንደዚያው ነው፡፡
የአዋዋጥን ጥበብ ለማድነቅ ከፈለጉ፣ ሕፃን ልጅ በማንኪያ ስታጐርሱት ምን እንደሚያደርግ ተመልከቱ፡፡ በምላሱ ምግቡን ወደ ውጭ ገፍቶ ያስወጣዋል፡፡ ለምን መሰላችሁ? ወደ አየር መተላለፊያ እንዳይገባ የሚያደርግ የአዋዋጥ ስልት ገና በሚገባ ስላልተካነበት ነው፡፡
ምንጊዜም ምግብ ሲበሉም ሆነ ፈሳሽ ሲጠጡ፣ ከአፍ ጀርባ፣ ምግቡም ሆነ መጠጡ ወደ አየር ቧንቧ እንዳይሄድ ዘግተው የሚከላከሉ አስገራሚ ሕይወት አዳኝ የሰውነት ክፍሎች አሉ፡፡ የሚበሉትንና የሚጠጡትን ነገር ለመዋጥ ሲዘጋጁ፣ Soft Palate የተሰኘው አካል ይመጣና ወደ አፍንጫ የሚወስደውን መተላለፊያ ይዘጋል፡፡ ወደ ሳንባችን እንዳይገባ ደግሞ Epiglottis ይከላከላል፡፡

የሆድ ውስጣዊ ግድግዳ ራሱን ያድሳል
የሆድ ግድግዳ በየሳምንቱ እንደሚታደስ ያውቃሉ? ሆዳችን፣ ሃይድሮክሎሪክ አሲድ የተባለ ኃይለኛ አሲድ የሚውልበትና የሚያድርበት ቤት ነው፡፡ አሲዱ ምግብን ሰባብሮ ይበልጥ እንዲብላላ ይረዳል” አሲዱ ከባድ በመሆኑ፣ ብረት የማቅለጥ አቅም አለው፡፡ የጨጓራ ጡንቻ በአሲድ እንዳይጎዳም ነው፤ የሆዳችን ግድግዳ በአራት ወይም በአምስት ቀን ራሱን የሚያድሰው፡፡

አጥንት
እንደ ብረት ጠንካራ፤ እንደ አሉሚኒየም ቀላል የሆነው አጥንታችን፣ ሕይወት አልባ ምሰሶ ነገር ወይም ድጋፍ አይደለም፡፡ የራሱ የደም ስርና ነርቭ ያለው ሕያው አካል ነው፡፡ በየጊዜው ሳያቋርጥ ራሱን ያድሳል፡፡ የአዋቂ አጥንት በየዓመቱ 10 በመቶ ያህል ራሱን ይተካል፡፡

የምድር ወገብን በእግር መዞር
ጤነኛ ሰው በአማካይ በየቀኑ ከ8 እስከ 10ሺህ እርምጃዎች ይጓዛል፡፡ በ70 ዓመት የምድርን ወገብ አራት ጊዜ እንደዞረ ይቆጠራል፡፡

50 ሚሊዮን ያህል የቆዳ ሴሎች ይሞታሉ
በየደቂቃው ከ30 እስከ 40ሺህ የቆዳ ሴሎች ይሞታሉ፡፡ ቆዳዎ፣ በየቀኑ 50 ሚሊዮን ያህል የሞቱ ሴሎችን ያስወግዳል ማለት ነው፡፡
ከሰውነት ክፍሎች ሁሉ ትልቁ አካል ቆዳ ነው ሲባል ሰምተው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በርካታ ጠቃሚ ነገሮች ስለሚሠራ ነው፡፡ 5 ሴንቲ ሜትር በ5 ሳንቲ ሜትር ስፋት ያለው ቆዳ፤ 650 የላብ ዕጢዎች፣ 9 ሜትር ያህል የደም ስሮች፣ 60ሺህ ቀለም አመንጪ ሴሎችና ከአንድ ሺህ በላይ የነርቭ ሴሎች ጫፍ አሉት፡፡
ምንጭ
Reader’s nigest - September 2013
By Dr. Traris Stork

Published in ህብረተሰብ

             “የስደተኛው ማስታወሻ” የተባለውን የተስፋዬ ገ/አብ አዲስ መጽሃፍ “በብላሽ” ወስጄ አነበብኩት። መጽሃፉን በነጻ የበተነው እራሱ ነው ይላሉ። አንድ ሰው የለፋበትን ነገር በነጻ ሲሰጥ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። በተለይ ደግሞ እንዲህ አይነት አወዛጋቢ መጽሃፍ ሲሆን ይበልጥ ያስጠረጥራል። ከዚያም አልፎ አንዳንድ ሰዎች የሚሉትን ያጠናክራል። ተስፋዬ ደግሞ አሳታሚዎቹ “ጫልቱ እንደ ሄለን” ብዬ የጻፍኩትን ምዕራፍ አውጣ ስላሉኝ ነው ይላል።
ለማንኛውም ዛሬ ይህንን አወዛጋቢ መጽሃፍ ከሌላ ማእዘን ለመዳሰስ እሞክራለሁ። የተስፋዬን ስራዎች ከ-እስከ አንብቤአለሁ። ብዙ ቃለ መጠይቆቹን ሰምቼዋለሁ። በተደጋጋሚ ፓል ቶክ ላይ ሲያደንቁት፤ ሲያሞካሹት፤ ሲያፋጥጡት፤ ሲያበሻቅጡት እና ሲከሸክሹት አድምጫለሁ። የግል ድረ ገጹ ላይ የሚያትማቸውን ጽሁፎች ተሸቀዳድሜ አንብቤዋለሁ። በአላማው ሲጸና አይቻለሁ። ኮፍያ ሲቀያይር ታዝቤያለሁ። ሲገለባበጥ ተመልክቼዋለሁ። አሪፍ መልስ ሲሰጥ ሰምቻለሁ። ሲምታታበት አስተውያለሁ። ፈንጂ ሲረግጥ አይቻለሁ። እንደ ሀር ተለሳልሶ ሲያመልጥም ተገርሜያለሁ።
ስለዚህም የተስፋዬ ጉዳይ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት አምናለሁ።
ተስፋዬ “አሊጎሪካል” ጸሃፊ ነው። ማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት በአሊጎሪ (ተምሳሌት) ይገልጻል። በዚህም የበአሉ ግርማ ተጽእኖ በደንብ ይታይበታል። በእርግጥ አሊጎሪ ጥሩ ዘይቤ ቢሆንም የተስፋዬ ግን ይበዛል። ሁሉን ነገር ተምሳሌት ማድረግ ያምረዋል። በእያንዳንዱ ትረካ ውስጥ ስለ መልእክቱ መጨነቁ ይታያል። ለመልእክቱ የበዛ ትኩረት በመስጠቱ የመጽሃፉን ርእስ የማይመጥን ትረካ አጭቆበታል። የስደትን ጉዳይ ችላ በማለት ብዙ ቅንጥብጣቢ አሊጎሪካል ታሪኮች አካቷል። ከአንዱ ወደ ሌላው የሚያደርገው ሽግግርም ድምዳሜውን (conclusion) ቀድሞ ይዞ የሚደግፍበት ታሪክ የሚፈልግ አስመስሎታል። ታሪኩ ከመልዕክቱ ጋር አልገጥም ሲለው ደግሞ “የደራሲነት ስልጣኔን ተጠቅሜ አስተካክዬዋለሁ” ይላል። ለማንኛውም ብዙ ርእሶችን ቢያነሳም ማስተላለፍ የሚፈልገው መልዕክት ግን ከአራት ወይም ከአምስት የሚበልጥ አይመስልም። ከዚህ ውስጥ የማንነቱ ጥያቄ ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

1. የማንነት ጥያቄ
የሰው ማንነት የሚገነባው በትውልድ አካባቢው ባህል (ቋንቋ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ሥነ ጥበብ…) ነው። ተስፋዬ በደም ኤርትራዊ ቢሆንም ያደገው ቢሾፍቱ ነው። ስለዚህ የተስፋዬ ማንነት የተገነባው በቢሾፍቱ ባህል ነው። ተስፋዬ ከኤርትራዊነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነቱ ከፍተኛ ነው። እንደዛም ቢሆን ግን የተስፋዬ ማንነት እስከ ዛሬ ድረስ በጣም አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል። ኤርትራዊ ደም ስላለው ብቻ ብዙዎች አያምኑትም። “ኤርትራዊ ሆነህ ለምን ስለ ኢትዮጵያ ትጽፋለህ?” ተብሎ እስኪሰለቸው ተጠይቋል። በዚህ ምክንያት የማንነት ጥማት ያጋጠመው ይመስላል። አብዝቶ ስለ ቢሾፍቱ የሚጽፈው ከዚህ ጥማት የተነሳ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ይህ የማንነት ጥማት በአብዛኛው ስደተኛ ዘንድ የሚያጋጥም ነው። የተስፋዬ ደግሞ የባሰ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ፓስፖርቱን በመነጠቁ ነው። በእርግጥ ፓስፖርቱን ቢያጣም ኢትዮጵያዊ ማንነቱን እንዳላጣ ለማሳመን የመጽሃፉን ሰባት ምዕራፎች ቢሾፍቷዊ አድርጎቸዋል።
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ኢትዮጵያ የነፈገችውን ማንነት ከኤርትራ ለማግኘት ይጣጣራል። “የወደዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይቀላውጡ” መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው። ኢትዮጵያዊ አይደልህም ሲባል ኤርትራዊነቱን ማንቆለጳጰሱ አይገርምም። ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያን እና ኤርትራን በማወዳደር የተጠመደው። ውድድሩ ከታዕታይ ምስቅልቅል (inferiority complex) የመጣ ማካካሻ (coping mechanism) መሆኑ ነው። ይሄ ደግሞ በተስፋዬ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ ኤርትራዊያን ስደተኞች ዘንድ የተለመደ ሽምጠጣ ነው። ከዚህ ባሻገር ግን “የኤርትራ ሰላይ ነው” የተባለው ብዙም ውሃ አይቋጥርም። በእርግጥ የሚያውቀውን መረጃ ሁሉ ለወዲ አፎም እንዳስረከበ ግልጽ ነው። የወቅቱን መረጃ ግን ሊያገኝ አይችልም። ስለዚህ ሰላይ ነው ብዬ አላምንም።

2. ኢትዮጵያ እና ኤርትራ
ተስፋዬ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በብዙ ነገሮች ያወዳድራል። አንዳንዴ እንደ ህጻን ልጅ ብሽሽቅ ውስጥ ይገባል። ለምሳሌ ኤርትራ ከደርግ የተገነጠለችው በሻእቢያ የውጊያ ብቃት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገልጻል። ኢህአዴግ ባይኖር ሻዕቢያ ዘላለም መገንጠል አለመቻሉን ሽምጥጥ ያደርጋል። ይህንን ለማስረዳት በርካታ ታሪኮች ጽፎልናል።
- የጄኔራል ታሪኩ ዓይኔን ግድያ በስማ በለው መረጃ ላይ በመመስረት “ከሻዕቢያ ጋር እንደራደር በማለቱ” እንደሆነ ሊያሳምነን ይሞክራል።
- ውድድሩን በመቀጠልም “አጸደ አደዋ” የተባለች ታጋይ ታሪክ አንስቶ የህወሃት ሰራዊት የትም የወደቀ መሆኑን ለማሳየት ሲጠቀምባት፤ “ጥቁር ጽጌሬዳ” በሚለው ቀጣይ ምእራፍ ውስጥ ደግሞ የኤርትራዊቷን ወጣት ምቾች እና ውበት ያሳየናል።
- እናት አገር ኢትዮጵያን “በአባት አገር ኤርትራ” ተክቶ አንድ ምእራፍ ሰጥቶ ያሳየናል።
- ሁላችንም የምናውቀውን መለስ ዜናዊ ስል ኦሮማይ መጽሃፍ የሰጠውን “ትርጓሜ” በአንድ ምእራፍ
አድምቆ ተርኮታል።
- የንስር አሞራው ታሪክ እና የኦርዮሌዎቹ ታሪክ በማምጣት የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ጦር እንድሚያሸንፍ ሊያሳምነን ይጥራል።
እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ታሪኮች መተረክ የፈለገበት ምክኒያት ኢትዮጵያ የኤርትራን አይበገሬነት አምና መደራደር እንዳለባት ለማሳየት ይመስላል። ለነገሩ የሱማሊያዊው ስደተኛ ህጻን (ማሊክ) ታሪክም ተመሳሳይ ነው። ተስፋዬ ለማሊክ ኳስ ገዝቶለት እንዳታለለው ኢትዮጵያም ጥቂት ነገር በመስጠት የሱማሊያን ችግር መፍታት ትችላለች ይለናል። ሱማሊያ የሚለው ኦጋዴንን ይሁን ወይም ሞቃዲሾን አይገልጽም። የቀጠናው ችግር ግን ተስፋዬ እንደሚለው ቀላል አይደለም።

3. የጫልቱ ግርግር
ተስፋዬ እንደሚለው ከሆነ መጽሃፉ በነጻ የተበተነው በምእራፍ ሰባት ምክንያት ነው። በእውነቱ “ጫልቱ እንደ ሄለን” የሚለው ምእራፍ እንዴት አዋራ ሊያስነሳ እንደቻለ አልገባኝም። ሁላችንም ተመሳሳይ ታሪኮችን እናውቃለን። እንዲህ አይነት ታሪክ ተፈጽሞ አያውቅም የሚል ሰው ገጥሞኝ አያውቅም። ግን በደፈናው ለምን ጻፈ የሚል ተቃውሞ በብዛት አንብቤያለሁ። የጫልቱ ታሪክ መታተሙ በሁለት ምክንያት ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ። የመጀመሪያው ሃሳብ በነጻነት እንዲገለጽ ስለምፈልግ። ሁለተኛው ችግሮችን በማለባበስ ትክክለኛ መፍትሄ ይመጣል ብዬ ስለማላምን ነው።
በእርግጥ የጫልቱ አይነት ችግር በዚህ ዘመን እጅግ ቀንሷል። ታዲያ ተስፋዬ ለምን ከዚህ ሁሉ አመት በኋላ ሊጽፈው ፈለገ? ታሪኩ ከስደተኛነቱ ጋር የሚያይዘው ምንም ጉዳይ የለም። ይህንን ታሪክ በመጽሃፉ ውስጥ እንዲካተት የፈለገበት ትልቅ ምክንያት እንዳለው አስባለሁ። ከነዚህም አንደኛው ተስፋዬ እራሱን እንደ ኦሮሞ ስለሚቆጥር፣ የኦሮሞን ችግር ማስተጋባት እንዳለበት በማመኑ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በፊት ለሰራው ስራ በውጪ የሚኖሩ የኦሮሞ መብት ታጋዮች “ኦቦ” የሚል ማእረግ እንደሰጡት ነግሮናል። በተጨማሪም ከተስፋዬ አጻጻፍ ተነስተን ጫልቱን በገሃዱ አለም ብንፈልጋት የምናገኛት ይመስለኛል። የጫልቱን ታሪክ ተስፋዬ በደራሲ ብእሩ እንደለወጠው ጽፎዋል። ይህም ማለት ጫልቱ በዚህ ዘመን ያለ ሰውን ታሪክ እንድትወክል ተፈልጓል ማለት ነው። ከዚህ በመነሳትም የጫልቱ ሚደቅሳ ታሪክ፤ የብርቱካን ሚደቅሳ ታሪክ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ምክንያቱም ብርቱካን ኦሮሞ መሪ ሆና የአማራ ማንነት እንደሸፈናት ጽፎ አንብቤያለሁ። መቼም ተስፍሽ “Conspiracy theory” በጣም ይወዳል። የ”ሰው ለሰው” ድራማ መሪ ተዋናይ የሆነው አስናቀ፤ መለስን የሚወክል ነው ሲል ከርሞ ነበር። ወዲያው ግን የአስናቀ ሚስት አዜብን አትመስልም በማለት ነገሩን አፍርሶታል።

4. የታሪክ እና የሃይማኖት ክለሳ
ተስፋዬ በአዲሱ ማስታወሻው አይነኬ አርዕስቶችን አንስቷል። ማንሳት ብቻ ሳይሆን ዘርጥጧቸዋል። ታሪክ እና ሃይማኖትን በተመለከተ ጥልቅ ጥናት ቢያስፈልግም ተስፋዬ ግን በድፍረት ብቻ ተጋፍጦታል። ይህ ትክክል አይመስለኝም።
የአቡነ ተክልዬን ገድል መሰረት የሌለው ነው ለማለት ሞክሯል። በዛም ሳይገደብ የፕሮቴስታንትን “ጌታ ተናገረኝ” የሚሉት ከህሊናቸው ጋር እያወሩ ነው ብሏል። በእርግጥ “የፍቅር በለጠ” ታሪክ በጣም አስቂኝ ነው። የፍቅር እየሱስ “ስለ ቁሳቁሶች ዋጋ ለመንገር የሚሯሯጥ የንግድ ወኪል” ይመስላል ብሏታል። እውነትም እንዲህ አይነት አማኞች ያሉ ይመስለኛል።
በተጨማሪም እኛ ኢትዮጵያዊያን ስለ አካል ጉዳተኞች ያለንን አመለካከት በሚገባ ተችቶበታል። “የጨለለቃ ዝይ” እና “ደስተኛ ዝይ” በሚለው ጽሁፉ ውስጥ ይህንን በደንብ ማየት ይቻላል።
ተስፋዬ ታሪክን ከአፈ-ታሪክ እያደበላለቀ ሊጋግረው ሞክሯል። እነዚህን ርዕሶች መፈተሹ ባልከፋ ነበር። ሆኖም ግን በጥልቅ ጥናት ላይ ተደግፎ እና ማስረጃውን አደራጅቶ ቢሆን ምንኛ ጥሩ በሆነ ነበር።
እነዚህ ሁሉ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንደ ችግር ተይዘው የበለጠ ጥናት ሊደረግባቸው እንደሚገባ የተስፋዬ መጽሃፍ ጥሩ ማመላከቻ ነው።
መጀመሪያ ባሳተመው “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” መጽሃፉ ላይ ላይ የነቆረውን የኢትዮ-ሚድያ ባለቤት አብርሃ በላይን ለመካስ እዚህ ግባ የማይባል የራያ ላይ ገጠመኝ በአንድ ምእራፍ አትሟል። እጅ መንሻ ካልሆነ ጥቅም የለውም። ከዚህም ሌላ በመጀመሪያ መጽሃፉ “ሙት” ብሎ ስላላገጠባቸው፤ ሁለተኛ መጽሃፉን በኢንተርኔት በተኑብኝ ካላቸው የኢህአፓ አባላት ጋር እሰጥ አገባው ቀጥሏል። በዚህ መጽሃፉ ውስጥ ኢህአፓን “ኢሃባ” በሚባል ውሻ መስሎ አቅርቦታል። “ኢሃባ” መልኩ የማይለይ የሰፈር ውስጥ ልክስክስ ውሻ ነው ይላል።
በእርግጥም ተስፋዬ በዚህ መጽሃፉ “ፈንጂ” ረግጧል። ይህ ጉዞው የት እንደሚያደርስው ወደፊት የምናየው ይሆናል።

 

Published in ህብረተሰብ

“በአንድ ቀን ትምህርት ፎቶ አንሺ ሆኜ ቁጭ አልኩ” - የ69 ዓመቷ አረጋዊ ወ/ሮ ባዩሽ

ካዛንቺስ አካባቢ በልመና የሚተዳደሩ አንድ አይነሥውር ሽማግሌ አሉ፡፡ የሚለምኑት ከካዛንቺስ ስድስት ኪሎና ፒያሳ ለመሄድ ታክሲ ከሚጠብቁ ተሳፋሪዎች ነው፡፡ አንድ ቀን በእለቱ የለመኑትን ገንዘብ ታክሲ እየጠበቅሁ ባለሁበት ቁጠርልኝ አሉኝ፡፡ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት አርባ ብር ለምነዋል፡፡ በሌላ ቀን ተመልሼ ጠየቅኋቸው። በልመና ከሚያገኙት ገንዘብ ልጃቸውን ኮሌጅ አስተምረዋል፡፡ ልጃቸው ሥራ ከያዘ ከዓመታት በኋላም ግን ልመና አላቆሙም፡፡ አሁንም እዚያው ካዛንቺስ እየለመኑ ነው፡፡
“ለምን ልመና አያቆሙም?” አልኳቸው፡፡
“ምን ላድርግ ቁጭ ልበል እንዴ?” በማለት እኔኑ መልሰው ጠየቁኝ፡፡ እዚያው ካዛንቺስ የሚለምኑ ሌላ አረጋዊ ከፍተኛ የእይታ ችግር አለባቸው፡፡ በምፅዋት የሚያገኙትን ሳንቲም ይዳብሱና አምስት ሳንቲም ከሆነ መልሰው ይወረውሩታል፡፡
በአንፃሩ የእይታም የአቅምም ችግር ያለባቸው የማይመስሉ አንዲት አሮጊት፤ ኡራኤል ቤተክርስትያን አካባቢ ከጥቂት ወራት በፊት አገኘሁ፡፡ የእሳቸው የአለማመን ዘይቤ ከተለመደው የተለየ ነው፡፡
“ቤቴ ልደታ ነው፤ መሳፈርያ አልያዝኩም” አሉኝ፡፡
“ኑ፤ እኔ እከፍልሎታለሁ፤ በዚያ አቅጣጫ ነው የምሄድው” አልኳቸው፡፡
“ባትሰጥ አትተወውም” ብለው እየተቆጡ ትተውኝ ሄዱ፡፡
ከቀኑ 11 ሰዓት ግድም ብሔራዊ ትያትር አካባቢ ሲለምኑ ያገኘኋቸው መስራት የሚችሉ ሴት ለልመናው ምክንያት የሰጡት “ልጄ ታሞብኝ ማሳከሚያ አጣሁ” የሚል ነው፡፡ እኒህኑ ሴት ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ኡራኤል ቤተክርስትያን አካባቢ ሲለምኑ አገኘኋቸው፡፡
አሁን ደግሞ “ገንዘቤን ዘረፉኝ” ሲሉ ሰማኋቸው፡፡
በየቦታው መሥራት እየቻሉ ልመና የወጡ አረጋውያን አያሌ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ አመል ሆኖባቸው ነው እንጂ ሠርተው በገቢ ራሳቸውን መደጐም ይችላሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል “ኸልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል”፣ የኢትዮጵያ አረጋውያን ማህበር እና ሌሎች አጋሮቻቸው ባለፈው ሳምንት አረጋውያን ሰርተው መጠቀም የሚችሉ መሆኑን የሚያሳይ የአራት ቀናት አውደርእይ ቦሌ አካባቢ በትሮፒካል ጋርደን ያዘጋጁት፡፡ ሰርተው ራሳቸውን በመደጐማቸው ደስተኞች መሆናቸውን ያነጋገርኳቸው አረጋውያን ይገልፃሉ፡፡
በ1993 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ አረጋውያን ማህበር፤ 38 አባል ማህበራት ያሉት ሲሆን “ጤነኛ አረጋውያን ሰርተው መኖር ይችላሉ” በሚል መርህ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ማህበሩ፤ በአረጋውያን ሊተገበሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን የሚቀርፅ ሲሆን አረጋውያንን በስልጠናና በልምድ ልውውጥ ያግዛል፡፡
የልምድ ልውውጡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ይከናወናል፡፡ ባለፈው ዓመት ለምሳሌ በእንግሊዝ የፖትስማውዝ ከተማ አረጋውያን ማህበር የአዲስ አበባ አቻውን ለልምድ ልውውጥ ጠርቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ለማህበሩ ፕሮጀክት ኦፊሰር ብቻ ሲፈቀድ የአረጋውያን ማህበር ፕሬዚደንቱ፤ “የከተማ ቦታ የለዎትም፤ ጡረታዎም ሃያ ፓውንድ አይሞላም፤ ሄደው ሊቀሩ ይችላሉ” በሚል የእንግሊዝ ኤምባሲ ቪዛ መከልከሉ ቅሬታ አሳድሯል፡፡ እናም የፖትስማውዙ ማህበር ለእንግሊዝ ፓርላማ ክስ አቅርቧል፤ ምላሹ ባይታወቅም፡፡ ቪዛ የተሰጠው ፕሮጀክት ኦፊሰር ግን እንግሊዝ ቀርቷል፡፡
የአረጋውያን ማህበር አባላት፤ ህብረተሰቡ ለአረጋውያን ያለው አመለካከት የተዛባ መሆኑ ችግራቸውን የከፋ እንዳደረገባቸው ይናገራሉ፡፡ ይሄን አመለካከት ለማስወገድም ትግል ላይ ናቸው፡፡ የህብረተሰቡ የተዛባ አመለካከት እንዲወገድ እየሰራን ነው የምትለው የ”ኼልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል” የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኤርና ምንተስኖት ሃንዝ፤ በአረጋውያን ላይ የሚደርስባቸው መብት ረገጣ እንዲቆም ፊርማ እያሰባሰቡ መሆኑንና ቅሬታቸውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚያቀርቡ ተናግራለች፤ ሕግ እንዲበጅለት፡፡በሰሞኑ አውደርእይ ብዙ መንቀሳቀስ የማይችሉ አረጋውያን አትክልት ውሃ ሲያጠጡ፣ ለራሳቸው ምግብ ለማሰናዳት ሽንኩርትና ድንች ሲልጡ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ቀርበዋል፡፡ ሥራዎቻቸው ከቀረቡላቸው ማህበራት አንዱ “እንረዳዳ” የአረጋውያን ማህበር ሲሆን አረጋውያን የተረጅነት ስሜት እንዳይሰማቸው እያደረግሁ ነው የሚለው ማህበሩ፤ የተወሰነ ሥራ እንደየአቅማቸው እየሰሩ መሆኑን ገልጿል፡፡ የማህበሩ አባላት የሰሯቸው የሽመና ውጤቶችም በአውደርእዩ ላይ ቀርበዋል። አረጋውያኑ እንደየስራቸው መጠንም ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ ጋቢ የሰራ የጋቢ ዋጋ፣ ፎጣ የሰራ የፎጣ ዋጋ ያገኛል፡፡ አባላቱ ዱቄት፣ ዘይት፣ ሳሙናና የመሳሰሉትም ይሰጣቸዋል፡፡ ተቀጥረው የመስራት አቅም ያላቸው ደግሞ በወጥ ቤትነት፣ በጥበቃ፣ በአትክልተኝነትና በፅዳት ሥራዎች እንደሚቀጠሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡የአረጋውያኑ ምርቶች ወደ ገበያው ገብተው የሚሸጡበት ሁኔታ የጠየቅኋት የአውደርዕዩ አስጐበኚ፤ “በባዛር እና በዕቁብ ይሸጣል፡፡ ለምሳሌ ብርጭቆ ፋብሪካ በወር ስምንት ጋቢ ይገዛል” ብላለች፡፡
የ75 ዓመቱ አረጋዊ አቶ መኩርያ፤ የጉለሌ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ በፊት ገበሬ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ሸማኔ ሆነዋል፡፡
በቀን ሦስት ክንድ እና ከዚያ በላይ እየሸመኑ በሳምንት አንድ ጋቢ እንደሚያደርሱ የተናገሩት አረጋዊው፤ “እኔ ተሯሩጬ መሸጥ ስለማልችል ማህበሬ ነው የሚሸጥልኝ” ብለዋል፡፡
ሌላው የ70 ዓመት አረጋዊ አቶ ኃይሌ ሀብተማርያም፤ ከበቾ አካባቢ ያርሱ ነበር፡፡ አቅም እያነሳቸው ሲሄዱ እየተረዱም ቢሆን አምራች አረጋዊ በመሆን አንዳንድ ወጪዎቻቸውን ራሳቸው እንደሚችሉ ገልፀውልኛል፡፡
“ውድ የአረጋውያን በጐ አድራጐት ድርጅት” በየወሩ ለእያንዳንዱ አረጋዊ 100 ብር የሚሰጥ ሲሆን አረጋውያኑ አትክልትና ፍራፍሬ በመነገድ ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ፡፡
የ69 ዓመቷ ወይዘሮ ባዩሽ ወልደአረጋይ፤ እድሜያቸው ሳያግዳቸው ፎቶ አንሺ ሆነዋል፡፡
“ፎቶ ማንሳት መቼ ጀመሩ?” ብዬ ጠየቅኋቸው፤ ወይዘሮ ባዩሽን፡፡ “እዚህ አረጋውያን ድርጅት ውስጥ እየሰራሁ “ኼልፕኤጅ ኢንተርናሽናል” ለልምድ ልውውጥ የውጭ ሰዎች አመጣ፡፡ በማግስቱ ካሜራ ሰጡን፤ ለማስተማር፡፡ እዚያው አስተማሩን። ሦስት አረጋውያን ነን በእለቱ ስልጠና የተሰጠን። አሰልጣኛችን እንዴት እንደምናነሳ አሳይቶን “ነገ ታሳዩኛላችሁ” ብሎ ሄደ፡፡ ራሳችን ያሳነውን የታጠበ ፎቶም ለኛ አሳይቶን ካሜራው ለእያንዳንዳችን ቀረ። ይኸውልህ ልጄ፤ በአንድ ቀን ትምህርት ፎቶ አንሺ ሆኜ ቁጭ አልኩ፡፡ ከዚያን ወዲህ ሠርግ ላይ ‘እቴቴ እስቲ ፎቶ አንሺን’ ተብያለሁ”
“እና ለወደፊት ምን አሰቡ ታዲያ?”
“ጥሩ ነው፤ ደግሞም ፎቶ እያነሳሁ ገንዘብ ማግኘቱም ይጠቅማል፡፡ እግዚአብሔር ካለ በዚህ ካሜራዬ ተአምር እሰራበታለሁ፡፡ ትልቅ ሥራ እሰራበታለሁ፤ ራሴንም እደጉምበታለሁ” ብለዋል፤ ወ/ሮ ባዩሽ፡፡ከ86 ሚ. የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ አምስት ሚሊዮን ያህሉ አረጋውያን እንደሆኑ የ”ኼልፕ ኤጅ” መረጃ ይጠቁማል፡፡

 

Published in ህብረተሰብ

     “ያኔ በኒው ኦርሊንስ ነገሮች አስቸጋሪ ነበሩ፤ እንኳንስ ለትምህርታችን ሊከፈልልን ይቅርና በልተን ካደርንም ዕድለኞች ነን፡፡ በህይወት መኖር እንቀጥል ዘንድ የሙዚቃ ፍቅር በደማችን ውስጥ ሊኖረን የግድ ነበር”
(ሉዊስ አርምስትሮንግ፤ የትራምፔት ተጫዋች)
አገሬ ምድር ላይ እያለሁ አገሬ የናፈቀኝ መሰለኝ፡፡ የማውቀው ሰው አጣሁ እንጂ፣ አገር ምድሩን ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ ህንፃዎቹ፣ ሙዚቃ ቤቶቹ፣ መንገዱ ወዘተ… አዲስ አልሆኑብኝም፡፡ ሠራተኛ ሰፈር፣ እሪ በከንቱ፣ ውቤ በረሃ፣ ዶሮ ማነቂያ፤ ገብረትንሳይ ኬክ ቤት፣ መሃሙድ ሙዚቃ ቤት፣ ሲኒማ አምፒርና ሀገር ፍቅር ቲያትር፣ ገበጣ መጫወቻ የሚመሳስሉ አስፋልቶች፣ ጣልያን የሰራቸው ጥንታዊ ፎቆች፣ ጣራቸው የዛገ አሮጌ ቤቶች … ቁጭ ፒያሳን - የሸገሯን። በአሜሪካ ኒው ኦርሊንስ ከተማ፣ በሉዚያና መንገድ እየተዘዋወራችሁ ዙሪያ ገባውን ስትቃኙ “ፒያሣ ነው እንዴ ያለሁት?” ብላችሁ መደናገራችሁ አይቀርም፡፡

በአሜሪካ ቆይታዬ እንደዚህች ከተማ ማንም ያደነጋገረኝ የለም፡፡ በነገራችሁ ላይ ኒው ኦርሊንስ የተቆረቆረችው በ17ኛው ክፍለ ዘመን ሉዚያና በተባለ ፈረንሳዊ የጦር አበጋዝ ነው፡፡
ከፒያሣ (ከራስ መኮንን ድልድይ እስከ ሲኒማ አምፒር) ያለው መንገድ በቸርችል ጎዳና፣ በቦሌ፣ በካዛንቺስ፣ በሜክሲኮ፣ በአራት ኪሎ፣ በጦር ሃይሎች፣ በመገናኛ፣ በጨርቆስ፣ በቺችንያ… በአዲስ አበባ ባሉ ሰፈሮች በሙሉ ሲዘረጋ፤ በደቡብ ምስራቅ ሉዚያና የምትገኘውን ኒው ኦርሊንስ ከተማ ይፈጥራሉ። ከተማዋ የአውሮፓውያን የስነህንፃ ጠበብቶች የእጅ ስራ ውጤት በመሆንዋ የተነሳ ‹‹በአሜሪካ የምትገኝ የአውሮፓ ከተማ›› እያሉ ይጠሯታል፡፡ ኒው ኦርሊንስ በዕድሜ ጠገብነቷም ሆነ በጥንታዊ ቤቶች ባለታሪክነቷ የሚወዳደሯት ሌሎች የአሜሪካ ከተሞች የሉም፡፡ ጥንታዊ ቤቶቿ እንደታሪክ መዘክር ስለሚቆጠሩ፣ ያለፈቃድ ማደስም ሆነ ንክች ማድረግ አይሞከርም፡፡
እቺ ጥንታዊና ታሪካዊት ከተማ እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም በሃሪኬን ካትሪና ክፉኛ ተመትታ እንዳልነበረች መሆኗን ነዋሪዎቿ ይናገራሉ፡፡ በአሜሪካ ታሪክ እጅግ አደገኛ የተባለው አውሎነፋስ ያናወጣት ኦርሊንስ፤ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ በአደጋው 1ሺ 700 ገደማ ሰዎች ሲሞቱ፣125 ቢ.ዶላር የሚገመት ንብረትም ወድሞባታል፡፡

ይሄ አደጋ ቀደም ሲል በከፍተኛነቱ ሪከርዱን ይዞ ከነበረውና ፍሎሪዳን ከመታው ሃሪኬን አንድሪው በአምስት እጅ ይልቃል ተብሏል፡፡ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የከተማዋ ክፍል በጐርፍ ተጥለቅልቆ የነበረ ሲሆን ከአደጋው በኋላም አገር አማን ሲሆን “በውሃ ላይ የቆመች ከተማ”፣ “የካትሪና ትራፊ” እና የመሳሰሉ ቅጽል ስሞች ወጥቶላታል፡፡ ሚሲሲፒ ወንዝን ከጐንዋ፣ ፓሲፊክ ውቂያኖስን እና የሜክሲካን ባህረ ሰላጤን ከግርጌዋ የተንተራሰችው ኦርሊንስ፤ በጥንት ጊዜ የባህር ላይ ዘራፊዎች “ዱር አገሬ” ብለው በመሸሸግ “አሸሼ ገዳሜ” የሚሉባት ከተማ እንደነበረች ይነገራል፡፡
የኒው ኦርሊንስ ሌላ መታወቂያ የጃዝ ሙዚቃ ነው፡፡ “የጃዝ ከተማ” ይሏታል፡፡ ከተማዋ አያሌ የጃዝ ሙዚቃ ቀማሪዎችን ፈጥራለች፡፡ ከ40 በላይ ታሪካዊ ሙዚየሞችን ይዛለች፡፡ የሆሊዉድ የፊልም መንደር ዋና መስሪያ ቤት በኒው ኦርሊንስ ነው። እ.ኤ.አ በ2012 መጨረሻና በ2013 ዓ.ም ከተሰሩ አስራ ሁለት ፊልሞች መካከል አስር ያህሉ በዚህች ከተማ ውስጥ የተቀረፁና በከተማዋ ላይ ያነጣጠሩ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነት ያህል ኦፕራ ዊንፍሬይ፤ የተወነችበት “ዘ ባትለርስ” ፊልም ይጠቀሳል፡፡ ኒው ኦርሊንስ የፀሐፊዎች፣ ሙዚቀኞች፣ ሰዓሊዎችና የፊልም ተዋናዮች መናኸሪያ ናት፡፡ የኢትዮ- ጃዝ አባት በመባል የሚታወቀው አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ፤ በየዓመቱ በከተማዋ በሚካሄደው የጃዝ ፌስቲቫል ላይ እንደሚገኝ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼ አጫውተውኛል፡፡

ባርበን ጐዳና
ባርበን ስትሪት (ጐዳና) ገብቶ ያልጠጣ፤ በማዲግራስ ያልተወዛወዘ፣ በዞሎ ዳንስ ያልተውረገረገ፣ በጃዝ ሙዚቃ ያልተመሰጠ፣ መጠጥ በእጁ ይዞ በዚህች ጐዳና ላይ ያልተንጐራደደ፣ ኦርሊንስን አውቃታለሁ ሊል አይችልም ይላሉ፤ ከተማዋን አብጠርጥረው የሚያውቁ ኢትዮጵያውያን፡፡ ከሠኞ እስከ ሰኞ ባርበን ጐዳና በላይቭ ሙዚቃ እየነጐነች ጠብቶ ይነጋል፡፡ ጐዳናው የመጠጥ ቤትና የሬስቶራንት ችግር የለበትም፤ በሽበሽ ነው፡፡ በአንድ ረድፍ ብቻ ከ40 በላይ መሸታ ቤቶች ተደርድረዋል፡፡ በሙዚቃ የሞቁና የደመቁ፡፡ ከትናንሽ ካፌዎች እስከ ስመጥር ሬስቶራንቶች ድረስ በዓይነት በዓይነት መመገብያ ማግኘት አይቸግርም።
ዓመታዊ ክብረ በዓሎችን የሚከበሩበት ዝነኛ ጐዳና ነው- ባርበን፡፡ ዓመታዊ የጃዝ ፌስቲቫል፣ ዓመታዊ የጥቁሮች በዓል፣ ዓመታዊ የተመሳሳይ ፆታዎች ክብረበዓልና ሌሎችም በድምቀት ይከበርበታል፡፡ ባርበን ቱሪስቶች ከሚርመሰመሱባቸው የከተማዋ ክፍሎች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ጐዳናው ሌላ የሚታወቅበት መለያም አለው፡፡ ለዓይን በሚዘገንን ቆሻሻና አፍንጫ በሚሰነፍጥ ክፉ ጠረኑ ይታወቃል፡፡ ይሄ የቱሪስት ጐዳና፤ የእኛን አገር አትክልት ተራ አስታውሶኛል - የፒያሳውን፡፡
የባርበን ጐዳና እንኳንስ ክብረበዓል ሲኖር በአዘቦቱም ቀን በቆሻሻና በትርኪምርኪ ከአፍ እስከገደፉ የሞላ ነው፡፡ የሲጋራ ወረቀቶች፣ ሶፍት፣ የፈረሶች ሽንት፣ የመጠጥ ፕላስቲኮች ወዘተ … ጐዳናውን በክለውታል፡፡ ዓይን ከሚቆረቁረው ጭስና አፍንጫ ከሚሰረስረው ጠረን በተጨማሪ የሰው ግፊያው የመርካቶን ገበያ ያስንቃል፡፡ በነገራችሁ ላይ የኒው ኦርሊንስ ፖሊሶች የፀጥታ ጥበቃቸውን የሚያከናውኑት በእግራቸው ወይም በቢኤምደብሊው ሞተራቸው ላይ ተፈናጠው አይደለም፡፡ ቢኤምደብሊው የሚያስከነዱ ሰንጋ ፈረሶች እየጋለቡ ነው፡፡
እነዚህ ፈረሶች ሽንታቸውን እንደ ዥረት የሚለቁት በአውራ ጐዳናው ላይ ነው፡፡ እንደ ፖሊስ ውሾች የሰለጠኑ አይደሉም፡፡ የእነሱ ሽንትና ሌላ ሌላውም ሲቀያየጥ የሚፈጥረውን “ኮክቴል ጠረን” ልትገምቱት ትችላላችሁ፡፡ የጐዳናው ጠረን ከመቅጽበት ጉንፋን የሚያሲዝና አላሳልፍ የሚል ቢሆንም ቱሪስቶች አካባቢውን ሲጠየፉት ወይም አፍንጫቸውን ሲይዙ እንኳን አይታዩም፡፡ በከተማዋ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ የታክሲ ሾፌር እንደነገረኝ፤ ቱሪስቶቹ ጠረኑ የተስማማቸው ነው የሚመስሉት፡፡ በጎዳናው ዘና ብለው ሲዘዋወሩ እንጂ ሲማረሩ ሰማሁ የሚል የለም፡፡ “ጠረኑ ሱስ ሳይሆንባቸው አይቀርም” ብሎኛል-የታክሲ ሾፌሩ።
ኒው ኦርሊንስ የጃዝ ሙዚቃ ከተማ ናት ብያችሁ የለ! ታዲያ ሙዚቃው ሁሉ ላይቭ (ህያው) ነው እንጂ ዲጄ የሚባል “ጨዋታ” የለም፡፡ የሙዚቃ ጠበብቶች የማንን ጎፈሬ ሲያበጥሩ?! ሙዚቃ በዲጄ ማጫወት በከተማዋ እንደ ነውር (taboo) የሚታይ ነው- ጥበብን እንደማርከስ ይቆጠራል። ሙዚቃው ሌት ተቀን ሲቀወጥ፣ የድምፁ ነገር እንዴት ይሆናል፤ ማንስ ማንን ያዳምጣል? ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ሁሉም እንዳሻው የሚለቀው ይመስላል እንጂ፤ የሚፈቀደው የድምፅ መጠን ይታወቃል፡፡ የተፈቀደውን ልክ ካለፉ ቅጣት ይከተላል፡፡ እንደኛ አገር በምንግዴ እስከ ጣራ ድረስ መልቀቅ ህገ ወጥነት ብቻ ሳይሆን ነውርም ነው፡፡ ከስንዴ መሃል እንክርዳድ አይጠፋምና ህግ ወጦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለእነሱ ግን ተቆጣጣሪዎች አሉላቸው፡፡ በየአካባቢው እየተዘዋወሩ የድምፅ መጠን በመለካት ህግና ስርዓት የሚያስከብሩ፡፡ ያለዚያማ የጩኸት ጎዳና ይሆን ነበር፡፡
ባርበን ጎዳና ለዓለማውያን ብቻ ሳይሆን ለመንፈሳውያንም ክፍት ነው፡፡ የሁለቱም ጐራ ተዋንያኖች ተቻችለው ዓላማቸውን ያራምዳሉ። ‹‹መንግስተ ሰማያ ደርሳለችና ንስሃ ግቡ!›› የሚል ማሳሰቢያ የሚለፍፍ ሃይማኖተኛ እንዲሁም የመፅሃፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እንደመፈክር ይዞ በመሃል ጐዳና የሚንጎማለል ሰባኪ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም - በነፃነት ጎዳናዋ ባርበን ስትሪት!
በተለይ ለአበሻ ‹‹አበስ ገበርኩ!›› የሚያሰኙ ትዕይንቶች ጐዳናዋን አያጧትም፡፡ ምን ጠፍቶ በባርበን ጎዳና!! በየመጠጥና ጃዝ ቤቱ በር ላይ የሚያማምሩ እንስቶች ተደርድረው ቆመዋል - እንደ ኤግዚቢሽን፡፡ ቆነጃጅቱ ለዓመል ያህል የጡታቸውን ጫፍ ከመሸፈንና ደልደል ያለ መቀመጫቸውን እንዲሁም ሃፍረተ ስጋቸውን በመናኛ ፒኪኒ ከመሰወራቸው በቀር፤ እርቃናቸውን ናቸው ቢባሉ ይሻላል፡፡ መለሎ ቁመናና ሰፊ ደረት ያለው ወንድ ደግሞ በፓንት ብቻ ቆሞ፣ 5 ዶላር ለሚከፍሉ ሴቶች ብልቱን አውጥቶ ያስጐበኛል፡፡ አብረውት ፎቶ የሚነሱም አሉ። የባሰባቸው ደግሞ እንዲያስነካቸው እየጠየቁ የፍላጎታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ሌላው ቢቀር ምናለ ጓንት እንኳን ቢኖር?!

ሮያል ስትሪት
ይሄ ጐዳና እጅግ ፀጥታ ያረበበበት ነው፡፡ “የጥበብ ጐዳና” እያሉ ይጠሩታል፡፡ ዝነኛ የዓለም ሰዓሊያን ተጠራርተው የመጡ በሚመስሉበት ሮያል ስትሪት፤ ሰዓሊያን ተደፍተው ከቀለም ጋር ይጫወታሉ፡፡ በሮያል ጐዳና የስዕል ስራዎች ከ20ሺ ዶላር ጀምሮ ይቸበቸባሉ፡፡ የስዕል ጋለሪዎች በሽበሽ ናቸው፡፡ ጊታር የሚጫወቱ ነጮች በየቦታው ተቀምጠዋል፡፡
ቱሪስቶችና ሙዚቃ አድናቂዎች ኪሳቸውና ቦርሳቸው ውስጥ ዘው እያሉ እጃቸው ያወጣውን ጣል እያደረጉላቸው ያልፋሉ፡፡ እንደኛ አገር የአዝማሪ ሽልማት መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ስላችሁ ግን ሙዚቀኞቹ ምንም የማያውቁ ምስኪኖች እንዳይመስሏችሁ፡፡ የሙዚቃ ሊቆች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼ እንደነገሩኝ፤ አብዛኞቹ የበርክሌ ዩኒቨርስቲ ምሩቃን ናቸው፡፡ በሮያል ስትሪት ሙዚቃ የሚጫወቱት የጥበብ ፍቅራቸውን ለመወጣት ነው፡፡ ከጥበብ በረከት ለመቋደስ!
የሰዎችን እጣ ፈንታ የምትተነብይ አንዲት ሴትም በዚሁ ጐዳና ላይ በስራ ተጠምዳ ስትባትል ታዝቤአለሁ፡፡ ጥንቆላ በሮያል ጐዳና ወደጥበብ ደረጃ ሳያድግ የቀረ አይመስለኝም፡፡ ሳይንስ ነው የሚሉም እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ ሳይንስነቱ እንኳን አልተዋጠልኝም፡፡

የድሆች ሰፈር (“ዘጠነኛው ዓለም”)
በከተማዋ ካስገረሙኝ ስፍራዎች መካከል የድህነት ወለል ወይም “ዘጠነኛው ዓለም” ተብሎ የሚታወቀው የጥቁሮች ሰፈር ነው፡፡ ወደዚህ ሰፈር ለመዝለቅ እንኳን እንግዳ ነዋሪዎቹም አይደፍሩም ተብያለሁ፡፡ አብዛኞቹ ባለታክሲዎች ዳጐስ ያለ ክፍያ ቢከፈላቸውም እሺ አይሉም፡፡ ብዙ ሰዎች ገብተው ቀልጠዋል ይባላል፡፡ በማን እንደተተኮሰ ባልታወቀ ጥይት ክልውት ያሉ መኖራቸውን ሰምቻለሁ፡፡ “ፖሊስ እንኳን ወደ አካባቢው ዝር አይልም” አለኝ፤ የታክሲ ሾፌሩ ጓደኛዬ፡፡ ይሄኔ የበለጠ ፈራሁኝ፡፡ ግን ደግሞ “ዘጠነኛው ዓለም” ምን እንደሚመስል ለማየት ክፉኛ ጓጉቼ ነበር፡፡
የታክሲ ሾፌር ወዳጄን እንደምንም አግባባሁት። እግዜር ይስጠው! ነፍሱን ሸጦ በታክሲው ወደ “ዘጠነኛው ዓለም” ይዞኝ ሄደ፡፡ ሰፈሩ ጭር ያለ ነው፤ የተወረረ ከተማ ይመስላል፡፡ አብዛኞቹ ቤቶች አሮጌና ጉስቁልቁል ያሉ ናቸው፡፡ እላያቸው ላይ ሳር የበቀለባቸው ሁሉ አሉ፡፡ ሰፈሩ የምርም ድሆች የከተሙበት ነው፡፡ ያጡ የነጡ ጥቁሮች የሚኖሩበት። ይባስ ብሎ እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም ከተማዋ በሄሪከን ካትሪና ስትመታ ክፉኛ ከተጐዱ አካባቢዎች አንዱ ነበር፡፡ እኒህ ጥቁሮች የሚኖሩት ከአሜሪካ መንግስት የሚያገኟትን የ180 ዶላር ወርሃዊ ድጐማ ብቻ እየጠበቁ እንደሆነ ወዳጄ አውግቶኛል፡፡ በሰፈሩ ውስጥ ለአራት ደቂቃ ያህል እየነዳን ከተመለከትን በኋላ ለመቀጠል አቅማማን።
ድንገት ወደ ጐን ዘመም ብሎ መስኮቱና በሩ ከተወለጋገደ ደሳሳ ቤት ታዛ ላይ ቁጭ ካለች ሴት ጋር ተፋጠጥን፡፡ ሴትየዋ በአራት ትናንሽ ጥቋቁር ህፃናት ተከባለች፡፡ ልጆቿ ሳይሆኑ አይቀሩም ብለን ገምተናል፡፡ ህፃናቱ ሲላፉና ሲሰዳደቡ ነበር፡፡
“ትሰሚያቸዋለሽ…በዚህ ዕድሜያቸው ብልግና እኮ ነው የሚሰዳደቡት” አለኝ - የታክሲዋን መዘውር የጨበጠው ጓደኛዬ፡፡ ከዚህ በላይ በአካባቢው ለመቆየት አልቻልንም፡፡ እንዳመጣጣችን ተመልሰን ወጣን - ከጐስቆላዋ የጥቁሮች ሰፈር፡፡ ይሄን ይሄን አሳይታኛለች ጉደኛዋ የኒው ኦርሊንስ ከተማ!

Published in ህብረተሰብ

          የጥቅምትን የመጀመሪያ ቅዳሜና እሁድ ያሳለፈኩት በናዝሬት ማለትም በአዳማ ከተማ ነው። እኔና ስምንት ዘመዶቼ ወደ አዳማ ያመራነው በአንድ እህታችን የጋብቻ ሥነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ነው፡፡ የናዝሬት ዘመዶቻችን አልጋ የተያዘልን መሆኑን አስቀድመው በስልክ ስለነገሩን፣ በቀጥታ ያመራነው አዳማ ጌጤ ሆቴል ጀርባ ገባ ብሎ ወደሚገኘው አባ ገዳ እንግዳ ማረፊያ ቤት ነበር፡፡ ናዝሬቶች፤ አልገዎቹ የተያዙት ለእኛ መሆኑን በመግለፅ፣ ከእንግዳ ማረፊያ ቤቱ ሠራተኞች ጋር አስተዋወቁንና፤ “እንደኛ ሆናችሁ አስተናግዱልን” በማለት አደራ ሰጥተው ወደ ፕሮግራማቸው ተመለሱ፡፡
የምሳ ሰዓት ደርሶ ወደ ሠርጉ ቦታ ከመሄዳችን በፊት አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ጊዜ ስለነበረን በየክፍላችን ገብተን አረፍ አልን፡፡ በኋላም ከየክፍላችን ተጠራርተን ወደ ምሳ ግብዣው ስናመራ “ምን የጐደለ አለ?” የሚል ጥያቄ ላቀረቡልን የእንግዳ ማረፊያ ቤቱ ሠራተኞች፤ “ከውሃ በስተቀር ምንም” የሚል መልስ እንደሰጠናቸው አስታውሳለሁ፡፡
የእራት ፕሮግራም የተዘጋጀልን በዚሁ በአረፍንበት ቤት ስለነበር፣ ወደ ቦታው የተሰበሰብነው በጊዜ ነው፡፡ ሁለት ሰዓት ላይ ራት በልተን ለሙሽሪት የዳቦ ስም የማውጣት ስርዓት ቀጠለ፡፡ የሙሽራው እናትና ዘመዶቹ ይሆናል ያሉትን ስም ሲሰጡ፣ የሰጡበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ “የለም እኔ የተሻለ ስም አለኝ” ያለው ስም ሲያወጣ፣ የእሱም በተራው ተቀባይነት ሲያጣ ቆይቶ የሙሽራው እናት ያወጡት ስም በደምቡ መሠረት ፀድቆ ዳቦው ተቆረሰና ተመራረቅን፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን የእንግዳ ማረፊያው ቤት ሠራተኞች አብረውን ነበሩ፡፡ እንግዳም አስተናጋጅም ሆነው እያገለገሉ ቆይተዋል፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት ግድም የናዝሬት ዘመዶቻችን ወደየቤታቸው ሲሄዱ እኛም ወደየመኝታ ክፍላችን ገባን፡፡ ከግማሽ ሰዓት በኋላ ያለሁበት ክፍል በር በኃይል ተደበደበ፡፡ በድንጋጤ በሩን ከፍቼ ወጣሁ።
“የአልጋ ሂሳብ አልተከፈለም” አለኝ፤ በር የደበደበው የአልጋ ክፍል ሠራተኛ፡፡
“እኛ አልጋ ተይዞላችኋል ተብለን ነው የመጣነው፡፡ ቀን ደግሞ አብረናችሁ ውለን አብረን አምሽተናል፤ ለምን አልጠየቃችሁንም?” አልኩ፤ እራሴን እየተቆጣጠርኩ፡፡ የአልጋ ክፍሉ ለጥያቄዬ መልስ ከመስጠት ይልቅ ገንዘቡን እንድከፍለው ብቻ መፈለጉን ከሁኔታው ተረዳሁ፡፡
“ነገ ጥዋት አልጋ የያዙልንን ሰዎች ጠይቀን፣ ካልከፈሏችሁ እንከፍላችኋለን” አልኩትና ወደ ክፍሌ ተመለስኩ፡፡
“የድርጅቱ ባለቤት ሳታስከፍሉ እንዳታሳድሩ ብሎናል” አለኝ፤ ሠራተኛው፡፡ እኔም ከመነታረክ ብዬ የራሴን ከፍዬ ወደ ክፍሌ ገባሁ፡፡
ከእኔ በኋላ የተቀሰቀሱት በየተራ እየተነሱ ከአልጋ ክፍል ሠራተኛው ጋር ክርክር ገጠሙ። እኔም ተመልሼ ከእነሱ ጋር ተቀላቀልኩ፡፡ እኔ በትዕግስት ያለፍኩት የበር ድብደባ ከሁላችንም መጨረሻ ለተቀሰቀሰው አሊ፣ በጣም የሚያበሳጭ ጉዳይ ሆነ፡፡
“ለምን በስርዓት አታንኳኩም? የእናንተን ብር ይዞ የሚጠፋ አለ?” አለ አሊ፤ በጣም እንደተቆጣ።
“ሳትከፍል ለማደር ነው የፈለግኸው” አለ ድንገት የደረሰው የአባ ገዳ የእንግዳ ማረፊያ ባለቤት፡፡
“ማን በነፃ አሳድሩኝ አላችሁ” አሁንም ይበልጥ እየተቆጣ አሊ ተናገረ፡፡ “አሁን መነጋገር አይኖርብንም፤ የሁሉንም እኔ ልከፍልህ እችላለሁ። አንተ ደረሰኝ ብቻ ስጠኝ፡፡ ነገ ከነሱ ጋር እንነጋገራለን” የአሊ መፍትሄ ነበር፡፡
ባለቤቱ ደረሰኝ በመጠየቁ የተደሰተ አይመስልም፡፡ እያጉረመረመ ሄደ፡፡ ወዲያው ግን ተመለሰ - የአባ ገዳ ማረፍያ ባለቤት፡፡ እናም በቁጣ ድምፀት “እንዲያውም አንተ አልቃኢዳ ልትሆን ትችላለህ! እዚህ ቤት አታድርም” ሲል አሊ ላይ አምባረቀበት፡፡
ሁላችንም መብረቅ የወደቀብን ያህል ነው የደነገጥነው፡፡ መጀመርያ ላይ ለምን እንዲህ እንዳለውም አልገባኝም ነበር፡፡ ድንጋጤዬ ሲቀንስልኝ ግን በስሙ የተነሳ እንደሆነ ገባኝ። በጣምም አዘንኩ፡፡ እንዲህ አይነቱ ፍረጃ በስንቶች ላይ እንደተፈፀመ፣ ወደፊትም ሊፈፀም እንደሚችል ሳስበው በጣም ከበደኝ፡፡ ቀጥሎ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ አሊን እየገፋሁ ወስጄ መኝታ ክፍሉ ውስጥ አስገብቼው ተመለስኩ፡፡
ጭቅጭቁን ለማብረድ ከመካከላችን አንዱ የአልጋውን ሂሳብ ከፈለ፡፡ የድርጅቱ ባለቤት ግን አሁንም በማን አለብኝነት መናገሩን ቀጥሏል፡፡
በሆቴል ቤቶች አካባቢ “ደንበኛ ንጉሥ ነው” ተዘውትሮ የሚነገር አባባል አለ፡፡
እኛን ግን እንኳን እንደ ንጉስ እንደ ሰው የሚቆጥረንም አላገኘንም፡፡
ባለቤቱ ገንዘቡን ተቀብሎ ሲወጣ የአልጋ ክፍል ሠራተኛውን ጠርቶ “ነገ አንድም ሰው ሳይቀር እንድታስወጣ፡፡ ማንም መቀጠል አይችልም!” በማለት ትእዛዝ ሰጠ፡፡ እኛም በነጋታው ለሁለት ቀን የተያዘልንን ክፍል ለቀን ወጣን፡፡
ማንም ሰው በሃይማኖቱ፣ በፖለቲካ አስተሳሰቡ ወዘተ መገለል ሊደርስበት እንደማይገባ በሕግ ተደንግጓል፡፡ እንዲህ አይነት በደል የደረሰበት ሰው መብቱን እንዴት ነው የሚያስከብረው?
ለአፍ ያህል “ደንበኛ ንጉሥ ነው” እያሉ ማጭበርበር ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ንጉሡ ተገቢውን መስተንግዶና አገልግሎት ማግኘት አለበት፡፡ በአባ ገዳ የእንግዳ ማረፊያ ግን “የንጉሡ ነገር” ተስፋ ያለው አይመስልም፡፡ ያሳዝናል፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 26 October 2013 13:52

“…አይወጣኝም ክፉ ነገር”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰላም ነው? ያው እንግዲህ ሰላምታችን “እንዴት ነው፣ በጎ አደርሽ ወይ…” “ትክትኩ ሌሊቱን ቀለል አለህ ወይ…” ምናምን መሆኑ ቀርቶ “ሰላም ነው?” በሚለው ከተጠቃለለ ሰነበተ፡፡
“ሰላም ነው?” ሲባል መልሱ “ምን ሰላም አለ ብለህ ነው?” እየሆነ… አለ አይደል… ዘመናችን በሰላምታችን ውስጥ እየተገለጸላችሁ ነው፡፡
ስሙኝማ…እውነትም ወደ ሚድል ክላስ መቃረባችንን የምናውቀው ሰላም ነው ከመባባል ወጥተን “እንደምን አደርክ?” “እግዜሐር ይመስገን…” ምናምን መባባል ስንጀምር እንደሆነ የሚሰማኝ ነገር አለ፡፡
እኔ የምለው…
ወደ መጣሁባት ምድር
እስክመለስባት በፍቅር
ሰውን ከማስደሰት በቀር
አይወጣኝም ክፉ ነገር፡፡
አይነት መልእክቶች ያሏቸው ክፉን ነገር “ጦሳችንን ይዘህ ሂድ…” ብለን የምናሽቀነጥርበት፣ ደጋጉን ነገር “እሰይ ስለቴ ሰመረ…” እያልን የምንቀበልበት ሥራዎች በዚህ ዘመን ምነው በብዛት አይሰሙምሳ! ነው…ወይስ ለ‘ቢዙ’ አይመቹም!
የምር ግን.. እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ክፉ ነገር’ የበዛ አይመስላችሁም? ማለትማ…አለ አይደል… ሁላችንም ለምን በትንሽ ትልቁ፣ ነገር ነገር እንደሚለን ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ከተማዋን ዘወር፣ ዘወር ስትሉ’ኮ እዚህም፣ እዛም… ትንቅንቅ፣ ግርግር፣ ጭቅጭቅ ማየት እየተለመደ ነው፡፡
በቀደም የነበርንበት ሚኒባስ ወደ ኋላ ሲሄድ የሆነን ሰው ለትንሽ ይስተዋል፤ ሰውየውም ሾፌሩን “አይተህ አትሄድም እንዴ” ምናምን ይለዋል። በዚሀ ጊዜ ሾፌሩ… ምን አለፋችሁ… በሰውየው ላይ ያዘነበበት ውርዥብኝ… “አዲስ አበባ ገዳይ ጠፋ እንጂ ሟችስ ሞልቶ ነበር… ያለውን የገጠር ሰው የሚያስታውስ ነው፡፡ ደግነቱ ሰውየው ነገሩን ሳያባብስ መሄዱ፡፡
ደግሞ ምን አለላችሁ መሰላችሁ…አንድ የሆነ ነገር ሲከሰት ሰዋችን ደግሞ ሦስት፣ አራት እየሆነ ከበብ፣ ከበብ ማድረግ እየለመደ ነው፡፡ የምር እኮ…ትንሿ ነገር አንድ መለስተኛ ዕድር ሊያቋቁም የሚችል ሰው ትሰበስባለች፡፡ እናላችሁ…አንዳንዴም በቀላሉ “አንተም ተው፣ አንተም ተው…” በመባባል ሊያልቁ የሚችሉ ነገሮች ‘አዳናቂ’ ይበዛና…‘ጎመኑ ይጠነዛል’፡፡
(እኔ የምለው… በከተማችን መኪና አሽከርካሪዎች መካከል ባለ የቃልና የምልክት ስድድብ… እኛን የሚስተካካል አገር አለ? የሚሰቀጥጥ እኮ ነው! “ጎረምሳ፣ ጎረምሳ የሚል…” ምናምን የለ፣ “ሦስት ጸጉር አብቅሎ አራተኛው እየተጠበቀ ያለ…” ምናምን የለ፣ “ገዳም በመግቢያ ዘመኗ…” ምናምን የለ፣ “አጎጠጎጤ እንኳን የሌላት ጩጬ”… ምናምን የለ…አገር ሲሰዳደብላችሁ ነው የሚውለው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ የ‘ጅምላ’ ነገር (‘ሞብ ሜንታሊቲ’ የሚሉት) አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ የሆነ ግርግር ነገር ሲሆን ባለጉዳይና ‘እበላ ባይ’ ይቀላቀልና ነገርዬው ሁሉ ይደበላለቃል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በየቦታው የምናየው አለመግባባት የሚባባሰው በሚመለከታቸው ሰዎች ምክንያት ሳይሆን በከባቢው ‘ሞብ’ ምክንያት ነው፡፡
እናማ…
…መጨቃጨቅ ይወገድና
ሰላም ይሁን ለሁላችን
መሰል መልእክቶች ያሏቸው ሥራዎች የሚያስፈልጉን ጊዜ ላይ ነን፡፡
ደግሞላችሁ…
ጥፋት እንዳለብኝ ይቅርታ
ንገረኝ ምንድነው ዝምታ
መሰል መልእክት ያላቸው ግጥሞች ዘንድሮ…አለ አይደል…በጣም በሚያስፈልጉን ጊዜ፣ ምነው ብዙም የማንሰማቸውሳ! ዘንድሮ የሆነ ጥፋት አጥፍቶ ይቅርታ መጠየቅ ‘ጎጂ ባህል’ አይነት ሆኗል። ልክ እኮ “ይቅርታ፣ አጥፍቻለሁ…” ማለት የራስን ‘ክብር’ ዝቅ እንደማድረግ አይነት ነው የሚመስለው፡፡ ከ‘ቦሶቻችን’ እስከ እኛ ተራዎቹ ድረስ…“ይቅርታ…” የሚለው ቃል ከመዝገበ ቃላታችን የጠፋ ይመስላል።
የሆነ መስሪያ ቤት ጸሀፊ የሰውየውን ስም ስትጠራ በተወሰኑ ቃላት ለውጥ ‘እትብቱ የተቀበረበትን’ ቦታ ወደሌላ ስፍራ ትወስደዋለች። እናማ…“ይቅርታ…” እንደ ማለት ጭራሽ ሳቋን ታስነካዋለች፡፡ ሰውየው ለአለቃዋ ይነግርና ሰው በተሰበሰበበት “ይቅርታ…” እንድትል ተደረገች፡፡
የስም ነገር ካነሳን አይቀር…ስሙኝማ፡፡ አንድ ሰሞን በአንዳንድ የዚቹ አገር ክፍሎች አገልግሎት ለማግኘት ስም እስከ አያት ድረስ ይጠየቅ ነበር አሉ። (አሁን ቀረ…ወይስ ብሶበታል?) ድካም ይሆናል እንጂ እናውራ ከተባለ እኮ ስንት የሚወራ ጉድ አለን መሰላችሁ! ይሄ የዘመድ አዝማድ አመላከከት ብዙ ቦታ እያስቸገረን ስለሆነ ነው የምንደጋገመው፡፡
እናማ…በየትኛውም ስፍራ ስም ሲወጣ ዋናው ምክንያት ለመለያነት ነው፡፡ አለቀ! ደቀቀ! ዮሐንስም ተባል…ቢቂላም ተባለ…ደንቦባም ተባለ…ሰጥአርጋቸውም ተባለ…ስም የአንድ ሰው መለያ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ምን መሰላችሁ…ዘንድሮ ስም ከመጠሪያነት አልፎ… አለ አይደል… ‘በር ለማስከፈት’ና ‘በር ለማስጠርቀም’ ምክንያት ሲሆን “ኧረ ምን እየሆንን ነው?” ያሰኛል፡፡ ባለፉት ዘመናት እንዲሀ አይነት ስምን ‘በር ለመክፈትና ለመጠርቀም’ መጠቀም የነበረ ቢሆንም…ዘንድሮ ታች፣ መንደር ድረስ መውረዱ ሊያሳስበን ይገባል፡፡
የምር እኮ…ካነሳነው አይቀር…ዘንድሮ ስለ አንድ ሰው ባህርይና አመለካከት አስተያየት የሚሰጠው በስም ሆኗል፡፡ “እከሌ ይባላል…” “እከሊት ትባላለች…” ሲባል ወዲያውኑ የሰውየውን ስም በተዘጋጀ የሀሳብ ፎርማችን ላይ እንሞላዋለን፡፡ ከዚያ በኋላ ሃሳብ የሚያሰጠው፣ ሥራ የሚያሠራው፣ ትችት የሚያሰማው፣ ድጋፍ የሚያደርገው…ምን አለፋችሁ…ሁሉንም እንቅስቃሴ የሚያደርገው ‘ሰውየው’ ሳይሆን ‘ስሙ’ ይሆናል፡፡
ብዙም ሩቅ በማይባል አንድ ጊዜ፣ አንድ የምናውቀው ሰው የሆነች እንትናዬ ላይ ‘ጆፌ ጥሎ’ ሲያንዣብብ ይከርምና ጫፍ ላይ ያርፋል። ቂ…ቂ…ቂ…(አሁን ልክ እኛ ዓለም ዋንጫ ‘ጫፍ’ እንደ ደረስነው!) ታዲያላችሁ…ይሄን ሁሉ ጊዜ የሚያውቀው ዋናውን መጠሪያ ስሟን ሳይሆን ‘ባክአፕ’ ስሟን ነበር፡፡ ታዲያላችሁ…አንድ ቀን እውነተኛ መጠሪያ ስሟን ከሌላ ይሰማል፡፡
እናማ… ምን ቢል ጥሩ ነው…“አንተ ያቺ እንትና ስሟ እንትና ነው እንዴ!” አለላችሁና…በቃ የፕሮጀክት ትግበራውን አቆመዋ! ስም…ለእንትንዬ ‘ነገራ ነገር’ እንኳ መመዘኛ ሲሆን አያሳዝንም!
ከዓመት ምናምን በፊት ለምሳ የሆነ ቦታ ገብተን አሳላፊ እስኪመጣ እንጠብቃለን፡፡ ያለማጋነን አምስት ደቂቃ ያህል ጠብቀናል፡፡ ወዲያው የሆኑ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እያወሩ ገቡ፡፡ ገና ተቀምጠው ሳያበቁ ሁለት አሳላፊዎች አጠገባቸው ደርሰዋል፡፡
እናማ…እንደ ስም ሁሉ የአፍ መፍቻ ቋንቋችን አገልግሎት ለማግኘትና ላለማግኘት ምክንያት ሲሆን በጣም፣ እጅግ በጣም ያሳዝናል። ለ‘አፋቸው ያህል’ እንኳን… “ይህ ጥሩ ምልክት አይደለም…” የሚሉ ‘ቦሶች’ በብዛት አለማየታችን ደግም…አለ አይደል…“አይ አንቺ አገር!” የማንልሳ!
እናማ…የከፉ የሚመስሉ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ ክፉ ነገሮች ‘ጦስ ጥምቡሳሳችንን’ ይዘው የሚሄዱበትን፣ ደጋግ ነገሮች ልባችንንና ቤታችንን የሚሞሉበትን ጊዜ ያፍጥልንማ!
ወደ መጣሁባት ምድር
እስክመለስባት በፍቅር
ሰውን ከማስደሰት በቀር
አይወጣኝም ክፉ ነገር፡፡
የሚለው ስንኝ የሁላችን ድምጽ የሚሆንበትን ጊዜም ያቅርብልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Page 2 of 16