በብሄራዊ መግባባት አጀንዳ ዙሪያ በነገው እለት በአዲስ አበባ ሠላማዊ ሠልፍ እንደሚያደርግ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፤ የሠላማዊ ሠልፉን መነሻ ብሄራዊ አካባቢ ከሚገኘው የፓርቲው ፅ/ቤት እንዳያደርግ በአስተዳደሩ መከልከሉን አስታውቆ፤ ክልከላው አግባብነት እንደሌለውና አስቀድሞ ባወጣው መርሃ ግብር የሠልፉን መነሻ ከ/ፅቤቱ እንደሚያደርግ ገለፀ፡፡ በሠላማዊ ሠልፍ መነሻና መድረሻ ጉዳይ ላይ የፓርቲው አመራሮች ከመስተዳድሩ የከንቲባ ቢሮ ሃላፊ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን ያመለከተው የፓርቲው መግለጫ፤ የሠላማዊ ሠልፉ መነሻና መቋጫ ጃንሜዳ ብቻ መሆን እንዳለበት በቃልና በደብዳቤ እንደተገለፀለት አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ “ክቡር የሠው ልጅ ቀርቶ እንስሣ እንኳ ጉዞውን የሚጀምረው ከቤቱ ወይም ከመኖርያ አድራሻው ነው” ያለው ፓርቲው፤ ሠልፉን ከፅ/ቤቱ አካባቢ ከመጀመር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ገልጿል፡፡ “ሠላማዊ ሠልፈኛ ዜጐቻችን የራሣቸው መሬት በስንዝርና በጭልፋ ተለክቶላቸው የሚሠጣቸው መሆን የለበትም” ያለው ፓርቲው፤ መስቀል አደባባይን ጨምሮ ሌሎች በአማራጭነት ያቀረባቸው የነበሩ ቦታዎች ከባቡር ግንባታው ጋር በተያያዘ ሣይፈቀድለት መቅረቱንና በሣር፣ በሙጃ እንዲሁም በሠንበሌጥ በተሞላው ጃንሜዳ ውስጥ ብቻ ሠላማዊ ሠልፉን እንዲያከናውን ትዕዛዝ እንደተላለፈለት አስታውቋል፡፡ የአስተዳደሩ ትዕዛዝ አግባብነት አለው ብለን አናምንም ያለው ኢራፓ፤ የሠላማዊ ሠልፉ መነሻ ብሄራዊ አካባቢ ከሚገኘው የፓርቲው ፅ/ቤት ሆኖ፣ መዳረሻው ጃንሜዳ ይሆናል ብሏል፡፡

Published in ዜና

            “ይማሩ የተባሉበት አዲስ ትምህርት ቤት መሰረተ ልማቶችን አላሟላም” ወላጆች በጉራጌ ዞን አበሽቲ ወረዳ የዳርጌ ቀበሌ የመሰናዶ ተማሪዎች በት/ቤቱ መሰረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው መስተጓጐላቸውን የተማሪዎቹ ወላጆች ተናገሩ፡፡ ከአንድ እስከ 10ኛ ክፍል በዳርጌ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ 11ኛ ክፍል ያለፉት ከ170 በላይ ተማሪዎች አዲሱ መሰናዶ ት/ቤት ገብተው ካልተማሩ የትም ሄደው መመዝገብ እንዳይችሉ ተደርገዋል ሲሉ የተማሪዎቹ ወላጆች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ “ከዚህ በፊት በዳርጌ ት/ቤት አስረኛን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ አስራ አንደኛ ሲያልፉ ወልቂጤ ከተማ የሚገኘው መሰናዶ ት/ቤት ውስጥ ይማሩ ነበር” ያሉት አንድ ወላጅ፤ በአሁኑ ሰዓት የተሰራው “ኮሌ” የተሰኘው መሰናዶ ት/ቤት ከመብራት በስተቀር እንደ ውሀ፣ ትራንስፖርት፣ የሚከራይ ቤት፣ እስኪሪብቶ ቢያልቅና ቢጠፋባቸው ወጥተው የሚገዙበት ሱቅም ሆነ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ስላልተሟሉለት ልጆቻቸውን ልከው ማስተማር እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ከዳርጌ ቀበሌ በ30 ኪ.ሜትር ከወልቂጤ ከተማ ደግሞ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ የተገለፀው አዲሱ የመሰናዶ ት/ቤት፤ ተማሪዎቹ ከወልቂጤም ሆነ ከዳርጌ በእግር ተመላልሰው ለመማር ሩቅ መሆኑን፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሌለውና ት/ቤቱ በሚገኝበት ቦታ የሚከራይ ቤት ባለመኖሩ ተማሪዎቹ በአማራጭ ማጣት እየተጉላሉ ነው ተብሏል፡፡

“ወልቂጤም ሆነ ወሊሶ ወስደን ልጆቻችንን ልናስመዘግብ ስንል ከዳርጌ ቀበሌ ከመጣችሁ አንመዘግብም እየተባልን ተቸግረናል” ብለዋል ወላጆች፡፡ “ችግራችንን ለሚመለከታቸዉ አካላት በተዋረድ አቤቱታ አቅርበናል” ያሉት አንድ ወላጅ፤ ከወረዳ ወደ ዞን፣ ከዞንም እስከ ክልል ድረስ የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ ሰዎች ተወክለው ቢሄዱም ምንም ምላሽ አለማግኘታቸውንና ልጆቻቸው የትምህርት ወቅቱ እየባከነባቸዉ መሆኑን በምሬት ገልፀዋል። የአካባቢው ሰው በራሱ ተነሳሽነት 500ሺ ብር አዋጥቶ አንድ ባለ አራት ክፍል ብሎክ ገንብቶ በማጠናቀቅ ላይ ቢገኝም የዞኑም ሆነ የወረዳው ት/ቢሮዎች አዲሱ መሰናዶ ት/ቤት ገብተው ካልተማሩ በስተቀር ወላጆች በገነቡት ት/ቤት ውስጥ ልጆቻቸዉን ማስተማር እንደማይችሉ እንደገለፁላቸው ወላጆች ተናግረዋል፡፡ የአበሽቲ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሰለሞን አበበ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ምላሽ በመስጠት ላይ እያሉ ስልካቸው የተቋረጠ ሲሆን በተደጋጋሚ ቢደወልላቸውም ከአገልግሎት ውጭ በመሆኑ ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡

Published in ዜና

የ“ላይፍ” መፅሄት ዋና አዘጋጅ አቶ ዳዊት ሰለሞን፤ በአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት በአቶ ፀሀይ ሽፈራው ክስ ቀረበበት፡፡ ላይፍ መፅሄት በመስከረም ወር እትሙ “የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት ኩብለላና ህገ ወጡ ብድር” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ ነው አዘጋጁ የተከሰሰው፡፡ ከትናንት በስቲያ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተጠርቶ ቃል የሰጠው ዋና አዘጋጁ፤ የባንኩ ፕሬዚዳንት “ስሜ ጠፍቷል” በሚል ክስ እንደመሰረቱበት እንደተነገረውና ቃል ከሰጠ በኋላ በአምስት ሺህ ብር ዋስ እንደወጣ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ አዘጋጁን ለክስ ያበቃው ዘገባ “አዋሽ ባንክ ሰራተኞቹ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ያዘጋጀውን ብድር አቶ ፀሀይ ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ለራሳቸው በመደበር እና ቤት ገዝተው አትርፈው በመሸጥ ተጠቃሚ ሆነዋል” የሚል ይዘት እንዳለው ታውቋል፡፡

“መረጃውን ያገኘነው ከአዋሽ ባንክ ሰራተኞችና ከውስጥ አዋቂዎች ነው” ያለው ዋና አዘጋጁ፤ ከሰራተኞቹ በተጨማሪ ነሀሴ 28 እና 29 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣም የፕሬዚዳንቱን እና የብድሩን ጉዳይ አስመልክቶ ተከታታይ ዘገባ አቅርቧል ብሏል፡፡ “አቶ ፀሀይ መፅሄቱን ሳይሆን ዋና አዘጋጁን ነው የከሰሱት” ያለው አቶ ዳዊት፤ ሁለት የሚዲያ ተቋማት አንድ አይነት ይዘት ያለው ዘገባ ሰርተው አንዱ ሳይከሰስ ሌላው የሚከሰስበት ሁኔታ እንዳልገባው ገልጿል፡፡

Published in ዜና

          ጠብት አምቡላንስ ዝቅተኛ ኑሮ እየኖሩ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ላመጡ ሃያ አራት የኮርያ ሠፈር ተማሪዎች የኑሮ ክህሎት (Life skill) እና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አሠጣጥ ስልጠና መስጠቱን እንዲሁም በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው የሚገለግሉባቸዉ ቁሣቁሶች መርዳቱን አስታወቀ፡፡ ተማሪዎቹ በአብዛኛው የኮርያ ዘማች ልጆች መሆናቸውን የገለፁት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ክብረት አበበ፤ ስልጠናውንና እርዳታውን መስጠት ያስፈለገው ማህበራዊ ግዴታን ከመወጣት አንፃር መሆኑን አመልክተው ለተማሪዎቹ የሻንጣ፣ የብርድልብስና የመማሪያ ቁሣቁሶች ከመለገሳቸውም በተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

በሃገሪቱ ባሉ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተመደቡት እነዚህ ተማሪዎች፣ በትምህርት ቆይታቸው የሚያስመዘግቡት ውጤት እየታየ ላፕቶፕና ኮምፒዩተሮችን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች በሽልማት መልክ እንደሚሠጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ ጠብታ አምቡላንስ የግል የአምቡላንስ አገልግሎት ሠጪ ድርጅት ሲሆን በሚሠጠው የመጀመሪያ ህክምና እርዳት እና የአምቡላንስ አገልግሎት ከተለያዩ ሃገር አቀፍና አለማቀፍ ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት ሽልማት ማግኘቱን ስራ አስኪያጁ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና
Page 16 of 16