ባለፈው ሳምንት አሜሪካ በነበርኩበት ጊዜ በላስቬጋስ የታወቀ ሆቴል ውስጥ የፋሺን ዲዛይን ስራዎቿን ስታቀርብ ያገኘኋትን ፍሬህይወት የተባለች ኢትዮጵያዊ ዲዛይነር በቃለ ምልልስ መልክ አስተዋውቄአችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ በኒው ኦርሊንስ፣ ጃክሰን ጐዳና ላይ ከበርካታ ዝነኛ ሠዓሊያን ጋር ሥዕል ሲስል ያገኘሁትን ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ አስተዋውቃችኋለሁ፡፡
ሠዓሊ ተስፋዬ ንጉሴ ይባላል፡፡ የተወለደው ወንጂ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የሥነጥበብ ት/ቤት በመግባት ለ5 ዓመት የሥዕል ትምህርት ተከታትሏል፡፡ ከዚያም “ኤርታሌ” የተባለ ስቱዲዮ ከፍቶ በሥዕል ስራ ላይ ተሰማራ፡፡ በሥዕል ስራ ገንዘብ ማግኘት የጀመረው ግን የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለ እንደሆነ ተስፋዬ አጫውቶኛል። በሥዕል ትምህርት ድግሪውን ከወሰደ በኋላም ለበርካታ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ካርቱኖችን ይሰራ ነበር። የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ነው ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ አሜሪካ ያቀናው፡፡ በዚያው አሜሪካ ቀረ፡፡
በጃክሰን ጐዳና በሥዕል ስራው ላይ ተጠምዶ ሳየው ላነጋግረው ፈለግሁና ቀጠሮ ያዝኩኝ፡፡ በቀጠሮአችን ዕለት መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ወዳለው የስዕል ስቱዲዮው ይዞኝ ሄደ፡፡ ገና መኖሪያ ቤቱ ስገባ “ትክክለኛ የሠዓሊ ቤት” አልኩኝ-ለራሴ። ቀለም … ብሩሽ … የስዕል ሸራ … የተለያዩ ሥዕሎች … ኮምፒውተር…የቀለጠ የሻማ ተራራ… ተመለከትኩኝ። በቀጥታ ወደ ቃለምልልሱ አልገባንም፡፡ ተስፋዬ ወጥቤት ገብቶ ምግብ ማሰናዳት ጀመረ፡፡ ሠዓሊነትና የምግብ ዝግጅት ሙያ ግንኙነት ይኖራቸው ይሆን? ብዬ እያሰብኩ ነበር ያሰናዳውን ምግብ ይዞ ከተፍ ያለው፡፡
ምግቡ ምን እንደሚባል ባላውቀውም በጣም ወድጄዋለሁ፡፡ ቅጠላ ቅጠል የበዛበት ምግብ ነው። ጣዕሙ ልዩ ነው፡፡ አቀራረቡ ይማርካል፡፡ እንደ ሥዕል በህብረ ቀለማት የደመቀ ነው፡፡ የምግቡን ስም ማወቅ ፈለግሁና ተስፋዬን ጠየቅሁት፡-
ምንም ሆነ ምን አንዴ በልተሽዋል፡፡ እንዳየሁሽ ደግሞ ወደሽዋል፡፡ ለጊዜው ግን ስም አልወጣለትም። የእኔ ፈጠራ ነው፡፡
(ከምግብ በኋላ እሱ ሸራው ላይ እየሳለ፣ እኔም ቃለመጠይቁን ጀመርኩ፡፡)
እንዴት ነው አሜሪካ ለሥዕል ስራ ትመቻለች?
አሜሪካኖች የፈጠራ ስራን በጣም ያከብራሉ። የሥዕል ስራዎችን በብዛት ይገዛሉ፡፡ ጃክሰን ስኩዌር (ጐዳና) አላየሻቸውም… ምን ዓይነት ሰዎች እንደሚመጡ? ሥዕል የሚገዙ አይመስሉም…ቱሪስቶች ናቸው፡፡ ግን ይገዙሻል፡፡ ጃክሰን ስኩዌር ትላልቅ ሥዕሎችን ይዞ ለመቀመጥ ቦታው አመቺ አይደለም፡፡ ትናንሽ ሥዕሎችን እየሰራን ነው የምንሸጠው፡፡ አንዱ ሥዕል ከ250-800 ዶላር ነው የሚሸጠው፡፡
ከሥዕል ስራ ውጭ የህንዶች ሱቅ ውስጥ ተቀጥሬ ማታ ማታ እሰራለሁ፡፡ በተረፈ ሥዕሎቼን በየመደብሩ እየዞርኩ አከፋፍላለሁ፡፡ ሰው የሚወዳቸውን ሥዕሎች እየሰራሁም አሳትሜ አዘጋጃለሁ፡፡ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ጃክሰን ስኩዌር ሄጄ ከሠዓሊዎቹ ጋር እሰራለሁ፡፡ ዝም ብለው ተራ ሠዓሊዎች እንዳይመስሉሽ፤ ዓለም አቀፍ ሰዓሊያን ናቸው፡፡
በሥዕል ሽያጭ ከብረሃላ?
ደሞ አገር ቤት ወዳጅ ዘመድ ሃብታም ሆኗል ብለው ያስቸግሩኛ! አየሽ…ፈጠራ ከተከበረ ልብሽም ይረጋጋል፡፡ እየተመሰጥሽ ፈጣሪንና አለምን አገናኝተሽ ቁጭ ነው፡፡ ሃብታም ሆነሃል ነው ያልሽው? ቆይ ሃብታም ነኝ እንዴ? ይመስገነው…በአለም መድረክ የአገሬን ስም ማስጠራት ችያለሁ። ከእውቅ ኢትዮጵያውያን አንዱ ሆኛለሁ፡፡ ከአለም ታዋቂዎች ጐራ እየተሰለፍኩ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ሥዕሌን ያዩና ይገረማሉ፡፡ አንድ ሰው ተሰጥኦው ኖሮት ትምህርት ካገዛው ምንም የማይሰራው ነገር የለም፤ ብዙ መስራት ይችላል፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ አጠገቤ ብዙ ሰዎች ስለነበሩ እየኮተኮቱ፣ ስራዬንና እኔን እያበረታቱ ነው ያሳደጉኝ፡፡ “አጥና” ስባል ወረቀትና እርሳስ ይዤ መሳል እጀምራለሁ፡፡ ለእኔ ጥናት ማለት እንደዛ ነበር፡፡
መቼ ነው መሳል የጀመርከው?
ሶስተኛ ክፍል እያለሁ ለተማሪዎች ሥዕል እሰራላቸው ነበር፡፡ አምስተኛ ክፍል ሳይንስ አስተማሪዬ በሥዕል ችሎታዬ ታደንቀኝ ነበር፡፡ ስድስተኛ ክፍል ስገባ፤ ዳይሬክተሩ ቀለም ይዞልኝ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተለያዩ የማስተማርያ ሥዕሎችን እስል ነበር፡፡ የልብ፣ የሳንባ፣ የኩላሊትና ሌሎች የሰውነት አካላት፡፡ ሰባተኛ ክፍል በፖለቲካ አስተማሪዬ አማካኝነት ሰሌዳ ላይ የሚለጠፉት ሥዕሎች ሁሉ የኔ ነበሩ፡፡ በቃ በትምህርት ቤት እየታወቅሁኝ መጣሁ፡፡ ለቤተሰብ ተደውሎ ቀለምና ከለሮች እንዲገዛልኝ ተነገረልኝ፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ስደርስ ሥዕል እየሰራሁ ገንዘብ ማግኘት ጀመርኩ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በሰራኸው ሥዕል ምን ያህል ገንዘብ እንዳገኘህ ታስታውሳለህ?
የሰው ፎቶግራፍ ስዬ ሃያ ብር ነበር ያገኘሁት። ሥዕል ጥርሴን የነቀልኩበት ሙያ ነው፡፡ ሠዓሊ ከሆንሽ ሌላ ነገር መሆን አትችይም፡፡ ትምህርት ስጨርስ አዲስ አበባ እህቴ ጋ መጣሁና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነጥበብ ት/ቤት ለአምስት ዓመት የሥዕል ትምህርት ተማርኩ፤ ማታ ማታ፡፡
ከትምህርት በኋላስ ምን ሰራህ?
ሠዓሊ ተፈሪ ከሚባል ጓደኛዬ ጋር “ኤርታሌ” የሚባል የሥዕል ስቱዲዮ ነበረን፡፡ በ90ዎቹ መጀመሪያ ይታተሙ ለነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች:- እነ ጦቢያ፣ ኢትዮጵ፣ ምኒልክ፣ አስኳል፣ ጐህ፣ መብረቅ፣ ሙዳይ፣ ጥንቅሽ፣ ጽጌረዳ፣ ቃልኪዳን…የመሳሰሉ ህትመቶች የስማቸውን ዲዛይን እኔ ነኝ የሰራሁላቸው፡፡ የርዕሰ አንቀፆችን ጽንሰ ሃሳብ ተቀብዬ ካርቱኖችንም እሰራ ነበር፡፡ ቦሌ ማተሚያ ድርጅትም ሰርቻለሁ፡፡
በአሊያንስ እንዲሁም፣ በሩሲያ የባህል ተቋም በተለያየ ወቅት ኤግዚቢሽን አቅርቤያለሁ፡፡ ሎሬት ጥበበ የማነህ ብርሃን፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ፣ እንዳልካቸው ተስፋ ገብረስላሴና ኃይሌ ገብረስላሴ ስራዎቼን ያደንቁልኝ ነበር። አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ከ10 በላይ ሥዕሎችን ገዝቶኛል፡፡ እንደውም ኃይሌ ምን እንዳለ ታውቂያለሽ? “አቅሙ ስለሌለኝ ነው እንጂ ብችል የአፍሪካ ሎሬት እለው ነበረ” ብሏል፡፡ ከእንግሊዝ የመጡ ጋዜጠኞች ፈረንሳይ ውስጥ ላለ መገናኛ ብዙሃን ቃለ መጠይቅ አድርገውኛል፡፡ ኤንቢሲ፣ ታይምስ፣ ቪኦኤ፣ ዶቼቬሌ፣ ኢትዮሚዲያ፣ ኢትዮጵያን ሪቪው…የዘገባ ሽፋን ሰጥተውኛል፡፡
እዚህ አገር ስንት ዓመት ቆየህ?
ስድስተኛ ዓመቴን ይዣለሁ፡፡ ኒውዮርክ፣ በርሊንግተን የሚገኘው ቬርሞንት ስቱዲዮ ሴንተር፣ በየዓመቱ ለ50 አገራት ስኮላርሺፕ ይሰጣል፡፡ ውድድሩ ቀላል አልነበረም፡፡ ቬርሞንት ስቱዲዮ ሴንተር ከሃምሳ አገራት አምስት መቶ ሠዓሊዎች ነው የሚጋብዙት፡፡ ከአምስት መቶ ሠዓሊዎች ጋር ለመፎካከር የግድ ችሎታ እና ብቃት ይጠይቃል። ሥዕሎቼን ልኬ ተወዳደርኩና አሸነፍኩ፤ ከዛም ስቱዲዮው ወጪዬን ሁሉ ሸፍኖ ኒውዮርክ አመጣኝ። በገባሁ በአራት ቀን ውስጥ አስራ ሁለት ሥዕሎች ሳልኩኝ፡፡ ከአገሬ ይዤ የመጣሁት ነበር የመሰላቸው፡፡ ማቴሪያሉን ቼክ አድርገው (ሥዕሉ የሚሰራበትን ጥሬ እቃ) በጣም ተገረሙ። የፋውንዴሽኑ ፕሬዚደንት (የሮክፌለር ታናሽ ወንድም ነው) ወዲያው ኤግዚቢሽን እንዳሳይ ፈቅዶልኝ፣ ሥዕሌን ከሰቀልኩ በኋላ እስከመጨረሻው ቀን ድረስ ሳይቀየር እንደ ነገ ልሸኝ እንደዛሬ ነው የተነሳው፡፡
ለአስራ አምስት ቀን ፒትስበርግና ሲሊቫኒያ ውስጥ ኤግዚቢሽን አቅርቤአለሁ፤ ለአለም አቀፍ ተመልካች፡፡ ቬርሞንት የዓለም ሠዓሊዎች መኖሪያ ከተማ ነው፡፡ ምን ተብሎ ይታሰባል መሰለሽ? “ሠዓሊዎች አንድ ቦታ ላይ ሲሰበሰቡ፤ አለምን የሚቀይር ትልቅ ሃሳብ ያመነጫሉ”፡፡ በነገርሽ ላይ ከእኔ በፊት አንድ አፍሪካዊ ብቻ ነው በዚህ ስፍራ ኤግዚቢሽን የማሳየት ዕድል ያገኘው፡፡ ከኢትዮጵያ ሠዓሊያን የመጀመሪያው እኔ ነኝ፡፡ በኤግዚቢሽኑ ላይ 21 ሥዕሎቼን የከተማው ከንቲባ ነበር የገዛኝ፡፡
ከኒውዮርክ ወደ ኒው ኦርሊንስ፣ ከሰሜን ተነስተህ ደቡብ ማለት ነው…እንዴት መጣህ?
አሜሪካ ከገባሁ ጊዜ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ሥዕሌ ላይ ነው የኖርኩት፡፡ በጣት የሚቆጠር ሰዓሊ ነው እንደዚህ አይነት እድል የሚያገኘው። ረዥም ሰዓት የማሳልፈው ሥዕሌ ላይ ነው፡፡ መጀመሪያ ከኒውዮርክ ፒተርስበርግ ነው የሄድኩት፣ ከፒተርስበርግ ዋሺንግተን ዲሲ፣ ከዛ ሜሪላንድ ገባሁ፡፡ አትላንታም ውስጥ ለአራት ዓመት ተቀምጫለሁ፡፡ አትላንታ የመጣሁት የቤተክርስቲያን ሥዕሎችን ለመስራት ጨረታ አሸንፌ ነው፡፡ የሰዓሊተ ምህረት ቅድስት ቤተክርስቲያንን ሥዕሎች ሠርቻለሁ፡፡ አትላንታን ሳየው ለሥዕል ጥሩ አገር መሆኑን ተገነዘብኩ፡፡ ፀጥ ያለ ነው፤ መኖሪያ ቤቶቹ ሰፋፊ ናቸው፤ ለስራ ይመቻሉ፡፡
እንዴት ወደዚህ ልትመጣ ቻልክ?
ኒው ኦርሊንስ የሚኖር ሬስቶራንት ያለው ጓደኛዬ ነው ከተማዋን እንዳይ የጋበዘኝ፡፡ ቤቱን ሲያሳድስ ሥዕሎች እንድስልለትም ፈልጐ ነበር፡፡ በኋላ ግን ልጁ ሃሳቡን ቀይሮ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። አገሩን ሳይ በጣም ደነገጥኩ…ለሰው ለማስረዳት ያስቸግራል፤ ኑ እና እዩት ከማለት በስተቀር፡፡ የሰው ልጅ ነጻ የሆነበት ከተማ ነው፤ መጨናነቅ የሌለበት፡፡ ወዲያው ተመልሼ ሄድኩና እቃዬን ሸክፌ እየከነፍኩ ወደዚህች ስቴት መጣሁ፡፡
እንዲህ ስላስደነገጠችህ ከተማ እስቲ በደንብ ንገረኝ …
ሲጀመር ይህቺ ግዛት የፈረንሳዮች ነበረች። ፈረንሳይ ና አርት ያላቸውን ቁርኝት ማንም ያውቀዋል፡፡ አርት በደማቸው ውስጥ ነው፡፡ ኒው ኦርሊንስ ሰው ሲፈጥር፣ መፃሕፍት ሲያገላብጥ፣ አዳዲስ ሃሳቦች ሲያንሸራሽር የሚኖርባት ከተማ ናት። የማየው ነገር ሁሉ ሥዕል ነው፤ ዕድሜ ይስጠኝ እንጂ የኒው ኦርሊያንስን ከተማ ስዬ የምጨርሰውም አይመስለኝ፡፡ የአሜሪካ ከተሞች ለእኔ ሙያ እንዴት ናቸው እያልኩ አንዳንዴ እየተቀመጥኩ፣ አንዳንዴ እግረመንገዴን ሳልፍ …የማየት እድሉ ነበረኝ፡፡ ግን እንደዚህ ዓይነት ጥንታዊና ለአርቲስቶች የሚመች ከተማ አላየሁም፡፡ የቤቶቹ ዲዛይን የሚገርም ነው። የምታያቸውን ቤቶች፣ አስፓልት፣ ድልድይ … ድንገት ብድግ ብለሽ ማደስ አትችይም፤ ክልክል ነው፡፡ ጥንታዊነታቸው ይፈለጋል፤ ይወደዳል፡፡ እዚህ አገር ሁሉም ቤት ዋይት ሃውስ ማለት ነው፡፡ የዛሬ ሁለት መቶ እና ሶስት መቶ ዓመት በልዩ ጥበብ የተሰሩ ናቸው፡፡ ቤቶቹን ብቻ በማየት የሚገኘውን ነገር…ሠዓሊዎች ይረዱታል፡፡ ስንማር እንደዚህ አይነት ቤቶችን ለማግኘት በጣም ከባድ ነበር፡፡ ጥንታዊ ቤቶችን እየፈለግን እንድንሰራ እንታዘዛለን፤ ዲኮራቲቭ ስለሆኑ፡፡ ዘይት ቀለም፣ ዋተር ከለሮች እዚህ እስከ ተፈጥሮዋቸው አሉ፡፡ በየመንገዱ ሙዚቃ ትሰሚያለሽ፡፡ ጃዝ አለ… ብቻ ምን ልበልሽ… በየመንገዱ በጊታር፣ በከበሮና በጃዝ አካባቢውን የሚያሳብዱት ተራ ሙዚቀኞች እንዳይመስሉሽ፡፡ በጣም ቶፕ (ታዋቂና ምርጥ) ሙዚቀኞች ናቸው፡፡ እዚህ ስቴት አንዴ ከታወቅሽ በቃ አገርሽ ይሆናል፡፡ ከ30-40 ሺህ የሚደርሱ ሠዓሊያን አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሠዓሊዎች አንዱ ብሆን ምን ዋጋ አለው። ከ40ሺ ሠዓሊዎች ጋር እየሰሩ መፎካከር ግን ምን ያህል ፈታኝና አጓጊ እንደሚሆን አስቢው፡፡
አሜሪካ ከመጣህ በኋላ የሥዕል ትምህርት ቤት አልገባህም?
ቀሽሞች ናቸው፡፡ አትላንታ “ዲኬተር አርት ኢንስቲቲዩት” ለአንድ አመት ሄጄ እንዳየሁት፣ ጊዜ ከመፍጀት በቀር አንዳችም የሚጨምርልኝ ነገር አላገኘሁበትም፡፡ ለምን መሰለሽ? እኔ ዕውቀት ነው የምፈልገው፡፡ እነሱ ደግሞ “በትርፍ ጊዜህ ተማሪዎችን አስተምርልን”፣ “አንዳንድ ነገር አግዘን” አሉኝ፡፡ ሥዕል ለመስራት ጊዜ የሚሻማብኝ ስለሆነ አልፈለግሁም፡፡ ከአገር ቤት የተለየ የትምህርት አሰጣጥ አላየሁበትም፡፡ እንደውም የወረደ ነው። የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች የተባሉትን ሳያቸው በጣም ነው ያፈርኩት፡፡ ከቀን ተማሪዎች ይልቅ የማታ የሚማሩት ይሻላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በሥዕል ሙያ ብቻ መተዳደር ከባድ ነው ይባላል፡፡ እዚህስ?
አየሽ..ይሄ አገር ያደገ ነወ፡፡ ኒው ኦርሊያንስ ሥዕል የሚከበርበትና የሚደነቅበት የጥበብ ከተማ ነው፡፡ እዚህ ሥዕል ሲገዙ በክሬዲት ካርድ ነው፡፡ ኦንላይን ነው አልኩሽ የምቸበችበው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ሁሉ የምታይው ሠዓሊ ሥዕል የሚስለው ፈቃድ አውጥቶ ነው፡፡ የሙያ ፈቃዳችንን ከጀርባ ሸጉጠን ነው የምንስለው፡፡ ተቆጣጣሪዎች እየዞሩ ፈቃድ ይጠይቃሉ፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ፈቃድ አንሰጥም፤ ሞልቷል ብለዋል፡፡ አንድ አርቲስት ኒው ኦሪሊያንስን አንድ ጊዜ ካየ፣ ሌላ የትም ቦታ ንቅንቅ አይልም፡፡ ለሠዓሊ የሚመች ከተማ ነው፡፡
ወደ ኒው ኦርሊንስ ስመጣ ያረፍኩበት ሰውዬ ባለ ሶስት ፎቅ ቤት ነበረው፡፡ ሁለቱን ፎቅ ለሶስት ወር ዘግቼ ሥዕል እንድሰራበት ሰጠኝ፡፡ ሰባ ሥዕል ነው ጨርሴ የወጣሁት፡፡ ኤግዚቢሽን እንዳሳይም አመቻቸልኝ፤ ከዛ በኋላ ጋለሪዎች፣ የሥዕል መደብሮች ሊያስቀምጡኝ ነው፡፡ ብዙ ስቴቶች ኤግዚቢሽን እንዳሳይ ጠይቀውኛል፡፡ ባለፈው ወር ዲሲና ኒውዮርክ አሳይቼ ነው የመጣሁት፡፡
ስራዎችህ ምን ዓይነት ጭብጦች ላይ ያተኩራሉ?
በአብዛኛው …ሰሚ አብስትራክ ናቸው፡፡ ኒው ኦርሊያንስ ከመጣሁ በኋላ ግን…እንደ ማዴግራ፣ ጃዝ፣ ዞዳ ዳንስ የመሳሰሉትን የዚህ አገር ሰው የለመዳቸውና የሚያውቃቸውን ታሪካዊና ባህላዊ የሆኑ ነገሮች አካትቼ ነው የምሰራው፡፡ እዛው ተስሎ እዛው ነው የሚሸጠው፡፡ በጃክሰን ስኩዌር ስንስል ያየሽን “ፓይረትስ” እንባላለን፡፡ እንደተመለከትሽን በአራት መዓዘን ዙሪያውን ከበን ነው የምንሰራው። በእኔ መስመር ያሉት ወደ አስራ ሁለት ይጠጋሉ። ከሩሲያ፣ ከጀርመን፣ ከኒው ኦርሊንስና ከተለያዩ ስቴቶች የመጡ ናቸው፡፡ ቦታው ላይ ፕሪንት አይሸጥም፤ እዛው ተስሎ እዛው ነው የሚሸጠው። ይሄንን የሚቆጣጠሩ አሉ፡፡ ይገርምሻል ስዬ የማልጨርሰው ሁለት ሳጥን ስኬች ነው ያለኝ፡፡
“ወዲያው ተስሎ ወዲያው” ስትል በትዕዛዝ ማለትህ ነው?
አዎ አንዳንዱ መጥቶ ያዝሻል…ላንድ ስኬፕ ስራልኝ፣ ፎቶ ስራልኝ ይላሉ፤ ቁጭ ብሎ ሳለኝ የሚልም አለ፡፡ ቤት ውስጥ የሰራኋቸውን ኦሪጂናል ሥዕሎች መግዛት የሚፈልጉ ስላሉ ይዣቸው እሄዳለሁ፡፡ ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ቱሪስቶች ስለሚበዙ ሥዕሎቹን ሲያይዋቸው ያውቋቸዋል። ከሥዕሎቹ ጋር በመንፈስ (spiritually) ነው የሚግባቡት፡፡
ሥዕሎችህ ኢትዮጵያዊ ባህል ወይም ታሪክ የሚያንፀባርቅ ነገር አላቸው?
ኢትዮጵያ እያለሁና ፒትስበርግ፣ ሲሊቫኒያ ከመጣሁ በኋላ የሰራኋቸው በከፊል የኢትዮጵያን ነገር ያንፀባርቃሉ፡፡ እዚህም ሆነ በየስቴቱ ፈረሶች የተለመዱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሥዕሎቼ ላይ ፈረሶች ይበዛሉ፡፡ አገር ቤትም እያለሁ ፈረሶች በብዛት እሰራ ነበር፡፡ ማንኛውም ሰው ይገዛቸዋል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የአድዋን ታሪክ ጠይቆ የሚገዛ አለ፡፡
ሰዎች ስለ ሥዕል ስራዎችህ ምን ዓይነት አስተያየት ይሰጡሃል?
በነገርሽ ላይ የአዲስ አበባ ስነጥበብ ትምህርት ቤት በአፍሪካ የመጀመሪያው የሥዕል ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ሥዕሎቼን በተመለከተ ብዙዎች በጣም ነው የሚደነቁት፡፡ “ኢትዮጵያዊ ሆነህ እንዴት እንደዚህ መስራት ቻልክ?” እያሉ በመገረም ይጠይቁኛል። ይሄን ለማስረዳት ይከብዳል፡፡ ግን የሚያሳፍረኝ ሳይሆን የምደሰትበት ነው፡፡ የትም ቦት ሄጄ ሰዎች በሥዕሎቼ ሲደነግጡ አስተውላለሁ፡፡
በቅርቡ ልትሰራ ያሰብካቸው ነገሮች አሉ?
ወደ ኒው ኦርሊንስ ከመጣሁ አምስት ወሬ ነው። ለፈረንጆች አዲስ ዓመት (በጃንዋሪ) ኤግዚቢሽን ላሳይ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ ስቶሮች (የሥዕል መሸጫ መደብሮች) ሥዕሎቼን በብዛት እንዳቀርብላቸው ይጠይቁኛል፡፡
በከተማዋ ውስጥ ባሉ መጠጥ ቤቶች (ባርስ) ብዙ ሥዕሎቼ ተሰቅለው ታገኛለሽ። ስሜና አድራሻዬ ተጽፎባቸዋል፡፡ ይሄንንም አይተው ነው “ፎክስ ቻናሎች” ደውለው ቃለ መጠይቅ ያደረጉልኝ። ኤግዚቢሽን ሳደርግ ሮጠው ነው የሚመጡት። በአለም አቀፍ መድረክ አገሬን ለማስጠራት ጥሩ አጋጣሚ እየሆነልኝ ነው፡፡

 

Published in ጥበብ

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የሰሜን ሸዋ ዞን፡ የቱሪዝም መስሕቦች ማጣቀሻ ዳይሬክተሪ አሳተመ፡፡ ከሐገሬ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ጋር በመተባበር ዞኑ ያሳተመው ዳይሬክተሪ፤ የአካባቢውን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መስሕቦች ዝርዝር የሚያካትት ነው፡፡ በአማርኛ ብቻ የተዘጋጀው ዳይሬክተሪው፤ የእንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ቅጂ በቅርቡ እንደሚዘጋጅለት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዞኑ ከያዛቸው ታሪካዊ ቅርሶች መካከል በጥንቷ ልቼ ከተማና በአንኮበር የሚገኙ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አብያተ መንግስት ይገኙበታል፡፡ የቱሪዝም ዳይሬክተሪው የዛሬ ሳምንት ይመረቃል ተብሏል፡፡

የኮሜዲያን አስረስ
በቀለ የሕፃናት መጽሐፍ ተመረቀ
“በፍቅር ላይ ሾተላይ” እና “የተወጋ ልብ” የተሰኙ ሁለት መጻሕፍት ነገ ከጧቱ 2፡30 በብሔራዊ ትያትር እንደሚመረቁ ዳኒ ሮጐ የማስታወቂያና ፊልም ፕሮዳክሽን አስታወቀ፡፡ በደራሲ ትክክል ገና የተፃፉት ሁለት የረዥም ልቦለድ መጻሕፍት በ2004 እና በ2005 የታተሙ ናቸው። በእውነተኛ ፍቅር ላይ ተመስርቶ የተፃፈው “የተወጋ ልብ”፤ 256 ገፆች ያሉት ሲሆን ዋጋው 40 ብር ነው፡፡ “በፍቅር ላይ ሾተላይ” 238 ገፆች ያሉት ሲሆን በተመሳሳይ ዋጋ ለገበያ ቀርቧል፡፡
በተያያዘ ዜና ዊዝ ኪድስ ዎርክሾፕ፤ “ፀሐይ መማር ትወዳለች” የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ድራማ እንዲሁም የልጆች መጻሕፍትን ዛሬ ከጧቱ 3 ሰዓት እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡ በብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት አዳራሽ የሚመረቁት ድራማና መጻሕፍት ዕድሜአቸው ከ3 እስከ 9 ዓመት ላሉ ሕፃናት የተሰናዱ ናቸው፡፡ ዊዝ ኪድስ ዎርክሾፕ የተለያዩ ዓለምአቀፍ ሽልማቶች እንደተሸለመ ይታወቃል፡፡
በሌላም በኩል “ቶላ አባ ፈርዳ” የተሰኘው የኮሜዲያን አስረስ በቀለ የሕፃናት መጽሐፍ ከትናንት በስቲያ ጧት አለምገና በሚገኘው አንኮር ሆቴል መመረቁን ስፖት ላይት የትምሕርት ማበልፀጊያ ማዕከል አስታወቀ፡፡ ኮሜድያን አስረስ ለአስራ ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ፕሮግራም ላይ በትወና፣ በድርሰት ጽሑፍ እና በአዘጋጅነት የሠራ ሲሆን “የቼሪ ማስታወሻ” እና “የአቶ በላቸው ጫማ” በተሰኙት የልጆች መጻሕፍቱም ይታወቃል፡፡

የደራሲና ዳይሬክተር ሱራፌል ኪዳኔ “ፍቅሬን ያያችሁ” ፊልም የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 11 ሰዓት በብሔራዊ ትያትር እንደሚመረቅ ወርቅ ሚዲያ ፕሮዳክሽን አስታወቀ፡፡ ለመሥራት አንድ ዓመት በፈጀው ፊልም መሐመድ ሚፍታ፣ ሩት አርአያ፣ እንግዳሰው ሀብቴና ሌሎችም ተውነዋል፡፡

በሠዓሊ ኤልያስ ሥሜ የተዘጋጁ የሥዕል ሥራዎች የሚቀርቡበት “የተወጠረ ገመድ” የሥዕል ዐውደርእይ ዛሬ በብሪቲሽ ካውንስል የሚከፈት ሲሆን አውደርዕዩ በጎተ ኢንስቲቲዩት፣ በአሊያንስ ኢትዮፍራንሴና በጣሊያን የባሕል ተቋም እንደሚቀርብም ታውቋል። የስዕል አውደርዕዩ በመስከረም አሰግድ ኩሬተርነት የሚቀርብ ነው፡፡ ሰዓሊ ኤልያስ ሥሜ ካሁን ቀደም በግሉ ዘጠኝ ዐውደርእዮች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ያቀረበ ሲሆን ከሌሎች ሠዐሊያን ጋር ደግሞ ስድስት ዐውደርእዮች አቅርቧል፡፡
በሌላም በኩል “የኢትዮጵያ ባሕላዊ የሥዕል ኤግዚብሽን” ከትናንት በስቲያ በላፍቶ አርት ጋለሪ ተከፍቶ መታየት እንደጀመረ ጋለሪው አስታወቀ። ሳር ቤት ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስትያን አካባቢ የተከፈተው ዐውደርእይ፤ አስር ሠዐሊያንን ያሳተፈ ሲሆን እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2006 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል።

የሴቶችን አቅም ለማሳደግ ያለሙ ዝግጅቶች በሸገር ኤፍኤም እንዲሁም በአማራ ክልል ሦስት ኤፍኤሞች እያቀረበ ያለው “የኛ” የሬዲዮ ፕሮግራም፤ ዛሬ በባሕርዳር ስቴዲየም የሙዚቃ ድግስ ያቀርባል፡፡ ከቀኑ ሰባት ሰአት ጀምሮ በባሕርዳር ስቴዲየም ለሕዝብ በነፃ የሚቀርበው የሙዚቃ ድግስ በዋነኛነት በልጃገረዶቹ የሙዚቃ ቡድን ይደምቃል፡፡ የልጆገረዶቹ የሙዚቃ ቡድን፤ ከአንጋፋዋ ዕውቅ ድምጻዊት አስቴር አወቀ ጋር ያዘጋጀውን የሙዚቃ ክሊፕም በቀጣዩ ወር ይለቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ “የኛ” ልጆች ያዘጋጁት ‘አቤት’ ነጠላ ዜማ ባለፈው ሳምንት “ምርጥ ነጠላ ዜማ” ተብሎ በሸገር ኤፍ ኤፍም የ “ለዛ” ፕሮግራም መሸለሙ ይታወሳል፡፡

Saturday, 19 October 2013 12:43

“ቢዝነሱ”

ከምሽቱ አንድ ሰዓት በመሆኑ የአራት ኪሎ ጉራንጉሮች በደንበኞቻቸው መጨናነቅ ጀምረዋል። ሰካራሙ፣ ወፈፌው፣ ቅንዝራሙ፣ መንታፊው፣ ለፍላፊው፣ ሴተኛ አዳሪዋ፣ ወንድ አዳሪው፣ ሎተሪና ቆሎ አዙዋሪው…የአራት ኪሎ ጉራንጉሮች ቁዋሚ ደንበኞች ናቸው፡፡ መንገዱም፣ ቤቱም፣ ድንግዝግዝ ያለ ነው - በአራት ኪሎ ሸለቆዎች፡፡
በአራት ኪሎ ጉራንጉሮች ውስጥ ሀፍረት፣ ይሉኝታ፣ ባህል፣ እምነት…እምብዛም ቦታ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ስርቆት፣ ዝሙት፣ ቅጥፈት፣ ውስልትና…የጉራንጉሮቹ መገለጫዎች ናቸው፡፡ አራት ኪሎ፤ ሞቃ፣ ግላ፣ ልትቀልጥ የምትደርሰው አመሻሽ ላይ በመሆኑ፤ ሲመሽ የነጋ፣ ሲነጋ ደሞ የመሸ ይመስላል፡፡ መንገዶችዋ የተጨናነቁ ናቸው፤ ኑሮ የተጨናነቀ ነው፡፡ ቤቶችዋ እጅግ የተጨናነቁ ከመሆናቸው የተነሳ፣ የሰው ሳይሆን የወፍ ጐጆ ይመስላሉ፡፡ የቤት ወጉ ሳይኖራቸው ቤት ተብለው ሰው ከሚኖርባቸው ውትፍትፍ ጐጆዎች አንድዋ የሃዳስ ገብሩ ክፍል ናት፡፡
የሃዳስ ክፍል፣ የተመረገችበት ጭቃ ወላልቆ በመውደቁ፤ በቡትቶ፣ በካርቶን እና በስሚዛ ቅጠል ተወታትፋ ላስተዋላት፣ ለሰው ሳይሆን፣ ለውሻ ማደሪያነት እንኩዋ፣ ብቃት የሌላት ትመስላለች፡፡ ክፍልዋ፣ ውስጥዋም እንደ ውጭዋ የተጐሳቆለ ነው።
ከአንድ የረጥባ አልጋና ከእንጨት ሳጥን በቀር ሌላ ንብረት አይታይም፡፡ ሳጥንዋ፣ የልብስ ማስቀመጫም ወንበርም ናት፡፡ ከሳጥኑ ጀርባ፣ በኮምፔልሳቶ የተጋረደች እጅግ ጠባብ ክፍል አለች - ጥቂት የሻይ ብርጭቆዎችና ባዶ የአረቄ ጠርሙሶች የሚቀመጡባት፡፡
ሀዳስ፤ እምብዛም ውብ፣ እምብዛም መጥፎ ያልሆነውን ጭንዋን በአግባቡ የሚያሳይ አጭር ጉርድ ቀሚስ ለብሳ፣ አምባሬጭቃዋን ተባብሳ፤ አንዴ ጐርደድ፣ እንደገና ቀጥ እያለች፣ እየተሽኮረመመች፣ እያሽኮረመመች፣ አላፊ አግዳሚውን ለመጥለፍ ያደረገችው ሙከራ አልሳካላት ስላለ፣ ደከማትና ወደ በርዋ ተመለሰች፡፡ “ምን አይነት ነጃሳ ቀን ነው? አስራ ሁለት ሰአት ሳይሞላ የወጣሁ እስከ አንድ ሰአት ድረስ እንዴት አንድ ሰካራም እንኩዋ አጣለሁ? ፎጋራ ቀን…” ባይሰማትም ምሽቱን ሰደበችው፡፡
በርዋን ተደግፋ ቆማ፣ የሰፈርዋን ሴቶች ስታይ፣ አንዳንዶች ከደንበኞቻቸው ጋር ቆመው “ዋጋ ጨምር፣ ቀንሽ” ይወጋወጋሉ፤ የቀናቸው፣ ይዘው ይገባሉ፡፡ ቀደም ብለው ያስገቡም፣ ቶሎ ብለው አስወጥተው፣ ሌላ ለመጥለፍ ይሽቀዳደማሉ፡፡
ሌሎች፣ እንዲህ አይነት እድል ሲገጥማቸው፣ እስዋ ለምን እንደሚጠምባት እያሰላሰለች፣ በጉዋደኞችዋ እየቀናች ሳለ፣ ጐረቤትዋን ሲያነጋግር የነበረ አንድ ጐረምሳ በአጠገብዋ ሲያልፍ አየት አረጋት፤ ጠቀሰችው፡፡ ዋጋ ጠየቃት፤ ነገረችው። ተስማሙ፡፡ ተከትሎዋት ገባ፡፡ ሞከረ፣ ግን፣ ሰውነቱን የሆነ ነገር ቀፈፈው፡፡
“ታረጋለህ አርግ፤ አለዚያ ውረድልኝ ሰውዬ” ሀዳስ ድንገት አንባረቀችበት፡፡
“ቆይ በእናትሽ? ስሜቴን አትዝጊው…” ኤፍሬም በማባበል ስሜት ጠየቃት፡፡
“ስሜት? እንዲህ አርጐም ስሜት የለ…” የሽሙጥ ሳቅ ሳቀችበት፡፡
“እንዴት ስሜት የለኝም!”
“ስሜት ታለህ ታዲያ ምን ያልፈሰፍስሃል?” በንቀት አየችው፡፡
“ማን ነው ልፍስፍስ?”
“እኔ ልበልህ ወንድም? ለጭቅጭቅ ጊዜ የለኝም፤ ከቻልህ አርግ፤ ካልሆነልህ ደሞ ውረድ” መረር አለችበት፡፡
“በእናትሽ አባብይው?”
“እ…? አባብይው? ማሙሽዬ አይዞህ … ባባ ኬክ ይዞልህ ይመጣል ልበለው?”
ምስኪንዋ ጐጆ እስከምትሰነጠቅ ሳቀችበት፡፡
“በእናትሽ? ትንሽ ሞክሪ?” ድጋሚ ተማፀናት፡፡
“ውረድ ልፍስፍስ…”
“ለምን ነው የምወርድ?”
“እና አዝየህ ላድር ነው? በቢዝነስ ቀልድ የለም፤ ይገባሀል?”
“ቢዝነስ? የቱ ነው ደሞ ያንች ቢዝነስ?”
“ሚስትህ መሰልሁህ? እየሰራሁ ያለሁትኮ ቢዝነስ ነው”
“ኧ…ሽርሙጥና በበረሃ ስሙ ሲጠራ ነው ቢዝነስ ማለት?” ኤፍሬም የፌዝ ሳቅ ሳቀባት፡፡
“በበረሃም ጥራው በደጋ ስሙ፣ ለኔ ቢዝነሴ ነው። ልቀቀኝ” ቀኝ እግርዋን ከራቁት ገላው ላይ አነሳች፡፡
“አንቺ እንቢ ካልሽ፣ ጉዋደኛሽን አላጣት፤ ምን ቸገረኝ፡፡ ብሬን መልሽልኝ”
“የምን ብር?” ተኮሳተረችበት፡፡
“የሰጠሁሽን አምስት ብሬን ነዋ”
“ኧረ ባክህ? እስካሁን ስታለፋኝ የቆየህ ያባትህ ቅሬላ መሰልሁህ” ኤፍሬም ተኝቶበት የነበረውን ግራ እግርዋን ለማስለቀቅ ታገለችው፡፡ ማንም እየመጣ ሲጨፍርባት የተሰላቸችው የረጥባ አልጋም አብራት ተነጫነጨች፡፡ “ልቀቀኝ ብዬሃለሁ ሰውዬ! ሁዋላ ትዋረዳለህ”
“ምን አባትሽ ልትሆኝ? ጥንብ ሸርሙጣ…” ኤፍሬም መልሶ ደፈቃት፡፡
“ሽርሙጥናዬን ፈልገህማ ነው የመጣኸው፤ ስብሰባ የተጠራህ መሰለህ? ባለጌ ልፍስፍስ! ወንድ ሆኜ ያንተን ድርሻ ላረግልህ ትፈልጋለህ? ሙትቻ! ወንድ ከሆንህ ያውልህ አርግ?” በጣትዋ ወደ ጭኖችዋ መሀል ጠቆመችው፡፡
ኤፍሬም የበታችነትና የመጠቃት ስሜት መላ አካላቱን ሲወርረው ተሰማው፡፡ እናም፣ ድንገት በጥፊ አጮላት፡፡ ሃዳስ፣ እየጮኸች እንደድመት ትቡዋጭረው ጀመር፡፡ እንደምንም ገፍትሮ ወደ አልጋዋ ጫፍ ጣላትና በችኮላ፣ ሱሪውን ከጣለበት ሳጥን ላይ ቢፈልገው አጣው፡፡
“ሱሪዬን የት አባትሽ ነው የደበቅሽው?”
“እበት ብላ! ጅል የወንድ አልጫ! ደሞ አንተ ምን ሱሪ አለህ?”
ኤፍሬም እንደ ገና በጥፊ ሲያልሳት፣ አራት ኪሎን በጩኸት አደበላለቀችው፡፡ ወዲያው፣ የሃዳስ ክፍል ወደ ሲኦልነት የተቀየረች መሰለች፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ፣ ምክንያቱን ያወቁትም ያላወቁትም፤ ብቻ የወሬ ሱስ ያለባቸው የአራት ኪሎ ሴትኛ አዳሪዎች፣ ጩኸቱንም ግርግሩንም እያባባሱት መጡ፡፡
ከአካባቢው የማይጠፉት የፖሊስ አባላት ግን፣ “የተለመደ የቁራ ጩኸት ነው” በማለት ነገሩን ችላ ብለውት ነበር፡፡ ሆኖም፣ ሃዳስ ቤት ሰው መገደሉን የስሚ ስሚ ሲሰሙ፣ በቸልታቸው ተፀፀቱና አካባቢውን በፍጥነት ተቆጣጠሩት፡፡
ፖሊሶች፣ ጩዋሂዋንም፣ አጩዋጩዋሂውንም እየገፈተሩ ከሃዳስ በር ሲደርሱ፣ ኤፍሬም ከወገቡ በታች እንደተራቆተ፣ እንጨት ሳጥኑ ላይ በአፍጢሙ ተደፍቶ፣ ደም እንደጐርፍ ሲወርደው አዩ፡፡
ሁለት የፖሊስ አባላት የኤፍሬምን አስከሬን በአንቡላንስ ይዘው፣ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ሲከንፉ፣ ሌሎች ግን፣ ወንጀለኛውን ለመያዝ፣ አራት ኪሎን ያተራምሱዋት ጀመር፡፡ ብዙም ሳይቆዩ፣ በርካታ ተጠርጣሪዎችን በመያዝ ወደ ጣቢያቸው ተመለሱና፣ የተለመደውን ምርመራ ቀጠሉ፡፡ ብዙዎችን የያዙዋቸው ቀድሞውንም ለማስረጃ ያህል ስለነበር፣ እንደነገሩ እየጠያየቁ፣ ወደ መቆያ ክፍል ላኩዋቸው፡፡ “ገዳዩ እሱ ነው” ተብለው በጥቆማ ከያዙት ዋናው ተጠርጣሪ ላይ ግን፣ ምርመራቸውን ጠበቅ አደረጉ፡፡
“ስም?” መርማሪ ፖሊሱ ጠየቀ፡፡
“የሰፈር ስሜን ነው ወይስ ዋናውን?”
“መ..ጀመሪያ የሰፈሩን ንገረኝ”
“ብዙ ነው”
“ለምሳሌ?”
“አሞራው፣ እ…ገንድስ፣ ቆሪጥ፣ አጅሬው፣ እ…ሌላም ይሉኛል፡፡ ግን ይኸ ሁሉ ለአንተ ምን ያረግልሃል?” ተጠርጣሪው መርማሪውን ጠየቀው፡፡
“ሌላ ማን ይሉሃል?” መርማሪው ያልሰማ መስሎ ጠየቀው፡፡ “አፍን”
“ሌላስ?”
“በቃ ይኸው ነው”
“ይሄን ሁሉ ስም ያወጣልህ ማነው?”
“ግማሹን ጉዋደኞቼ፣ሌላውን ደግሞ የሰፈር ሰው”
“ለምን ነው እንዲህ አይነት ስም ያወጡልህ?”
“በአንዳንድ ድርጊቴ…”
“ለምሳሌ?”
“አሞራው ያሉኝ ሞባይል ስለምሰራ ነው”
“መስራት ማለት?”
“ያው አንዳንድ ሰዎች ተዝናንተው በሞባይል ሲያወሩ ፣ነጥቄያቸው ስለምሮጥ እ…‹አፍን› ያሉኝ ደሞ፣ ሀርድ የምታበዛ ሴት ስታጋጥመኝ በግድዋ ስለማወጣት ነው፡፡ ብቻ፣ሰው ማካበድ ስለሚወድ፣ የሆነ ስራ ስሰራ፣ የሆነ ስም ያወጣልኛል” የተጠርጣሪው መዝናናት መርማሪውን አስገርሞታል፡፡
“እሺ ዋናው ስምህስ?”
“ወርቁ በላቸው”
“ያያት ስም?”
“የእናቴን ነው የአባቴን?”
“የአባትህ አባት..?”
“ገመቹ”
“እድሜ?”
“እድሜዬ?”
“አዎ እድሜህ ስንት ነው?”
“ሀያ አምስት ቢሞላኝ ነው”
“የትምህርት ደረጃህ?”
“አንድ ጊዜ ካራቴ ተምሬያለሁ”
“ማን ነው ያስተማረህ? የት ነው የተማርኸው?”
“ያስተማረኝ ‹ዘንጥል› የሚባል ጉዋደኛዬ ነው። የተማርሁት እንጦጦ ጫካ ውስጥ” የመርማሪው ጆሮዎች ይበልጥ ተቀሰሩ፡፡
“ዘንጥል ማነው? አሁንስ የት ነው ያለው?”
“ትላንት ደየመ፡፡ እንዴት ያለ ጎበዝ ልጅ ነበር መሰለህ!”
“በምን ምክንያት ሞተ?” መርማሪው እንደ ዋዘ ጠየቀው፡፡
“አንድ ከእሱ የባሰ ጉልቤ በስኪኒ ወጋና ገደለው። እኔ እንኩዋ ከእሱ ጋር መሳፈጥህን ተው ብየው ነበር”
“እሺ ስራ?”
“ምን አይነት ስራ?”
“ስራህ ምንድነው? ነው የምልህ!” መርማሪው በተሰላቸ አንደበት ጠየቀው፡፡
“የተገኘውን ነው የምሰራ”
“ለምሳሌ?”
“በቃ፣ ቋጠሮም ተገኘ ሌላ የጉልበት ስራ እሰራለሁ”
“የጉልበት ስራ ስትል?”
“ያው እ…ሞባይል፣ቦርሳ፣እ..አንዳንዴ ሀንግ…” አንገቱን በግዴለሽነት ሰበቀ፡፡
“ሞባይል፣ቦርሳ ትነጥቃለህ፡፡ ‹ሀንግ አረጋለሁ› ስትል ምን ማለትህ ነው?”
“ይህ ጠፍቶህ ነው? ያው ፍሉስ አለው ብዬ የገመትሁትን ሰው አፍኜ እዳብሰዋለሁ”
“እዳብሰዋለሁ?” መርማሪው ትኩር ብዬ እያየ ጠየቀው፡፡
“አዎ፣ ኪሱን እፈትሻለሁ”
“አልሰጥም ብሎ ቢታገልህስ?”
“ዋጋውን ያገኛላ”
“ማለት?”
“ኪል አረገዋለሁዋ”
“ጥሩ፣የቅድሙን ሰውዬ ታውቀዋለህ?”
“የቱን?”
“ሀዳስ ቤት ወድቆ የተገኘውን”
ከዛሬ በፊት አላውቀውም”
“ታዲያ ለምን መታኸው?”
“ሲመታት እያየሁ ዝም ልበል?”
“እንዴት?”
“እንዴትማ..ሲቅለበለብ መጥቶ፣ለሾርት አምስት ብር ከፈላት”
“እሺ..?” ፖሊስ እያንዳንድዋን ቃል በጥንቃቄ መመዝገብ ጀመረ፡፡
“ከዚያ፣ አልጋ ላይ ወጣና ቢለው፣ ቢለው አልቆምለት አለ፡፡ በዚህ የተነሳ፣ ብሬን መልሽልኝ አልመልስም፣ ከሀዳስ ጋር ጭቅጭቅ ጀመረና እንደማትመልስለት ሲያውቅ ይደበድባት ጀመር፡፡ በዚህ የተነሳ ያው…በቃ በቦክስ ስሰጠው ሳጥኑ ላይ ወደቀ”
“ሲመታት እንዴት አየህ?”
“እዚያው ነበርሁዋ”
“የት?”
“ከምስጢር ክፍልዋ”
“ከማን?”
“ከሀዳስ ነዋ”
“ምን ልትሰራ?”
“ቢዝነስ ነዋ”
“ምን አይነት ቢዝነስ?”
“ያው እሱ ችክ አገኘሁ ብሎ ሲያፎደፍድ፣እኔ ኪሱን እፈትሻለሁ”
“ብዙ ጊዜ እንዲህ ታረጋለህ?”
“አዎ በቸሰትሁ ጊዜ ሁሉ እሰራለሁ”
“ለመሆኑ ሀዳስ ምንህ ናት?”
“ሚስቴ”
“ሚስቴ?” መርማሪ ፖሊስ ተገረመ፡፡
“አዎ ሚስቴ፡፡ ምነው?”
“አንተ አልጋ ላይ ፣ሚስትህ ከሌላ ወንድ ጋር ስትተኛ ትንሽ አትናደድም?”
“ምን ሀርድ አለው? ነካው እንጂ፣እንዳለ ይዞብኝ አይሄድ፡፡ ወዲያውስ፣ቢዝነስ እኮ ነው”
“ቢዝነስ?”
“አዎና ቢዝነስ”
“እንዲህ የምታደርጉት ተስማምታችሁ ነው? ወይስ እያስገደድሀት?”
“ለምን አስገድዳታለሁ? ለቢዝነስ አይደል እንዴ ካገርዋ የመጣችው?”
“የፈፀምኩት ድርጊት ትክክል ነው ብለህ ታስባለህ?”
“ቢዝነስ ስትሰራ’ኮ፣ ያው መሳሳትህ አይቀርም”
“እና? ተሳስቻለሁ ነው?”
“ባልሳሳትም ያው መትቸዋለሁ፡፡ ፊልም አታይም እንዴ? ለቢዝነስ ሲባል ስንት ወንጀል ነው የሚሰራ?”
“እና ፊልም ላይ ያየኸውን ለመድገም ስትል፣ የምስጢር ቦታ አዘጋጅተህ ሚስትህን ከሌላ ወንድ ጋር እንድትማግጥ ታረጋለህ፡፡ በአጋጣሚውም ዘረፋ ታካሂዳለህ?”
“ዘረፋ አይደለም፤ ቢዝነስ ነው፡፡ ቆይ እስኪ? አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፤ ሚስት አለህ የለህም?”
“አለችኝ”
“ጥሩ፣ ስራስ አላት?”
“የላትም” ፖሊሱ መጨረሻውን ለመስማት ጓጓ።
“በጣም ጥሩ፣ ስራ ከሌላት መቼም ዝም ብለህ ስትቀልባት አትኖርም፡፡ ቀን ቀን ቢዝነስ ስትሰራ ብትውልኮ ማታ የአንተው ናት፡፡ እ….”
“በቃ…!”መርማሪው ድንገት አንባረቀበትና ወደ ማረሚያ ቤት ላከው፡፡

 

Published in ልብ-ወለድ

በ”የሕልም ሩጫ” ሲታወሱ
በ1895 ዓ.ም በ12 ዓመቴ ከአዲስጌ አዲስ አበባ መጥቼ ከዚህ ዓለም እሽቅድምድም ገባሁ። አንዱ ሲሾም ሌላው ሲሻር፣ አንዱ ሲታሰር ሌላው ሲፈታ፣ አንዱ ሲሞት ሌላው ሲተካ በማየት የዚህን ዓለም እሽቅድምድም ትግል አጠና ነበር፡፡ በ1895 ዓ.ም የምኒልክ ትምህርት ቤት ሲከፈት (ትምህርት ቤቱ 4 ኪሎ ከመምጣቱ በፊት ፒያሳ በአልፍሬድ ኤግል መኖሪያ ቤት እያለ ማለታቸው ይሆናል) ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን፣ ልጅ ብሩ ሃብተማርያም፣ እምሩ ኃይለሥላሴ፣ ዘውዴ ጐበና፣ አስፋው በንቲ፣ እኔና ሌሎች ልጆችም አብረን ነበርን፡፡
የአጐቴ ሞት ጥልቅ ሀዘን ላይ ስለጣለኝ 5 ዓመት በጽሞናና በብቸኝነት ተቀመጥኩ፡፡

“ፍላጐትህን ስታባርረው ተመልሶ እየጋለ ይመጣል” እንደሚባለው እሽቅድምድሙን ዓለም ተመልሼ ተቀላቀልኩ፡፡ በዚያ ዘመን ተወዳዳሪን ለማሸነፍ የቤተ - መንግስትን ሥርዓት ማወቅ ያስፈልግ ነበር፡፡ ባለማዕረግ አባት የሞተበት ልጅ በቀላሉ ወደ ስልጣን ይወጣል፡፡ እኔ አባቴ በልጅነቴ ስለሞተ ውድድሩን በጥረቴ ማሸነፍ ነበረብኝ፡፡ አፄ ምኒልክ ከሞቱ በኋላ ከልጅ ኢያሱ ጋር መግባባት ስላልቻልን ይኸም ተጨማሪ መከራ ሆነብኝ፡፡ ባለመሾሜ እኔ ብቻ ሳልሆን ወዳጆቼም ሀዘን ገባቸው፡፡ አለቃ ገብረሚካኤል ለሚባሉ አባት ጭንቀቴን ስነግራቸው:-
“አንድ ወዳጅህ የሆነ ሰው ምሳ ቢጋብዝህ ቁርስ ለመብላት ትሄዳለህን ወይስ ለራት ቢጋብዝህ ለምሳ ትሄዳለህ? እንደዚሁም ሁሉ እግዚብሔር በዚህ ዓለም ለሥራ የመረጠውን ሰው አንዳንዱ በጠዋት፣ አንዳንዱን በእኩለ ቀን፣ ሌላውንም በማታ ነው የሚጠራው፡፡ ምናልባት አንተ ለእኩለ ቀን ወይም ለማታ ተጠርተህ እንደሆን፤ ለጠዋት ካልሆነህ ብለህ በከንቱ ታዝናለህን?” አሉኝ፡፡ ምክራቸው ልቤን ነካኝ፡፡ እኔም ደጅ ጥናቱን ትቼ ቤቴ ተቀመጥኩ፡፡
በምኒልክ ትምህርት ቤት አብረውኝ የተማሩት ልጅ፤ አልጋ ወራሽ ሲሆኑ አለቃ ገብረሚካኤል የሰጡኝ ምክር ትዝ አለኝ፡፡ በወዳጄ ዘመነ መንግስት ከአስር የማያንሱ የስልጣን ማዕረጐችን አገኘሁ፡፡ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭም በተለያዩ ኃላፊነቶች እየተሾምኩ አገለግልኩ፡፡ በ1921 ዓ.ም በለንደን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆንኩ፡፡ በማይጨው ጦርነት ከንጉሱ ጋር አብሬያቸው ነበርኩ፡፡ ሚያዝያ 24 ቀን 1928 ዓ.ም ከኦጋዴን ጦር ሜዳ በጅቡቲ በኩል ወደ አውሮፓ ሲሄዱም በቅርብ ነበርኩ፡፡
በ1907 ዓ.ም የራስ ቢትወድድ መንገሻን ልጅ ዘውዲቱን አግብቼ ሰላምና ደስታ የሞላበት ትዳር ነበረኝ፡፡ ከጃንሆይ ጋር ወደ ውጭ በሄድኩበት ወቅት ታምማ አልጋ ላይ ነበረች፡፡ ዳግመኛ መገናኘት አልቻልንም፡፡ ሁለተኛው ትዳሬን የመሠረትኩት በኢየሩሳሌም ሲሆን ልዕልት የሻሽ ወርቅ ይልማን ነው ያገባሁት፡፡ በስደት ላይ እያለንም የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ተወካይ ሆኜ ወደተለያዩ አገር ባለስልጣናት እየሄድኩ ጉዳይ አስፈጽሜያለሁ ጠላት በተባረረ ማግስት በ1934 ዓ.ም የአገር ግዛት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሰብሳቢ ሆንኩ፡፡ በኢሊባቡር ጐሬ ተሹሜም ሠርቻለሁ፡፡ መፃሕፍትን መፃፍ የጀመርኩት እንደትርፍ ጊዜ ሥራ ነበር፡፡ ይህን “የሕልም ሩጫ” ብዬ የሰየምኩትን መጽሐፍ ያዘጋጀሁበት ምክንያት ሰው በነፍሱ አፈጣጠር ከፍ ያለ መሆኑን፤ በሥጋዊ አፈጣጠሩ ብልሹ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡
እግዚአብሔር ባንዱ እጁ አንዱን ዘመን ሲያጠፋ፣ በሁለተኛ እጁ ሌላውን ዘመን ያበራል። እድሜና ዘመን ከመሄድ አያቋርጡም፡፡ ሰውም የጊዜው ተገዢ በመሆኑ በሰከንድ፣ በደቂቃ፣ በሰዓት፣ በቀን፣ በወርና ባመት ላይ ተቀምጦ ይገሰግሳል፡፡ ማንም ባለስልጣን ሰው ቢሆን ነገን ጠልቸዋለሁና ልለፈው፤ ትላንትን ወድጄዋለሁና ልመልሰው ለማለት አይችልም፡፡ ስለዚህ በራስ ሃሳብና ምኞት መጣደፍ የሕልም ሩጫ፣ የማይጨበጥ አረፋ ይሆናል፡፡
የሰው ልጅ እንዳትክልት በሕፃንነቱ ለምልሞ፣ በወጣትነቱ አብቦ፣ በጐልማሳነቱ አፍርቶ ሲታይ ደስ እንደሚል እንደዚሁ በዕድሜ ጠውልጐ፣ በእርጅና ደርቆ፣ በሞት ሲቆረጥ የሰውን የመጨረሻ ዕድሉን ስናስበው በጣም ያስገርማል፡፡ ይህ ሲታይ ሰው በዚህ ዓለም ላይ ለጥቅምና ለክብር የሚደክመውና የሚሮጠው ሁሉ የሕልም ሩጫን ይመስላል፡፡
በስደት ላይ ሳለን ሥዕሎችንም እስል ነበር፡፡ ነፃነት ተመልሶ በአገራችን መኖር ስንጀምር ባለቤቴ ልዕልት የሻሽወርቅ ይልማ ሕፃናት መርጃ የበጐ አድራጐት ድርጅት መሥርታ ነበር፡፡ ስዕሎቼን በ2ሺህ 800 ብር ሸጨው ለበጐ አድራጐት ሥራው ውሏል፡፡ ከፃፍኳቸው መፃሕፍት አንዳንዶቹ ለቴአትር ጨዋታ ተጠንተው በመድረክ ሲቀርቡ በተገኘው ገንዘብ ሕዝብ ሲጠቀምበት ማየቴ የመንፈስ ደስታ ሰጥቶኛል፡፡ ለጃንሆይ 25ተኛ ኢዮቤልዩ በዓል፤በሥማቸው የተሰየመው ቴአትር ቤት ተመርቆ ሲከፈት የእኔ ቴአትር (ዳዊትና ኦርዮን) ተመርጦ በመቅረቡ ላቅ ያለ የመንፈስ ከፍታ ተሰምቶኛል፡፡
መጽሐፍ ከመድረስ፣ ሥዕል ከመሳል፣ የቴአትር ጽሑፎችን ከማዘጋጀቴም ባሻገር ለፎቶግራፍ ጥበብ ልዩ ፍቅርና አክብሮት አለኝ፡፡ በ “የሕልም ሩጫ” መጽሐፌ ውስጥ በርካታ ፎቶግራፎችን ያስገባሁት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ፎቶግራፍ ለአገርና ለሕዝብ ታላላቅ ተግባራትን አከናውነው ያለፉ ባለታሪኮችን ምስል የሚያኖርልን ሙያና ጥበብ ስለሆነ ሌሎች ሰዎችም ፎቶግራፎችን እንዲያስቀምጡ አደራ እላለሁ፡፡
ሕፃን ከእናቱ ማህፀን በኩል ወደዚህ ዓለም ላይ የሚመጣው ለመልካም ወይም ለክፉ መልዕክት እንደሆነ የታወቀ በመሆኑ፤ ፓስካል (Pascal) የሚባል የፈረንሳይ ሊቅ አንድ ሕፃን አልጋው ላይ ተኝቶ ሲንፈራገጥ ባየ ጊዜ፣ ባርኔጣውን አውልቆ “አንተ ሕፃን ለእንዴት ያለ ሥራ ተልከህ መጥተህ ይሆን?” ብሎ እጅ ነስቶት ያልፍ ነበር ይባላል፡፡
በምድር ሕይወት እንደምንመለከተው ራሱን በመጥላት፣ ወንድሙን በመውደድ፤ ገንዘቡንም ሕይወቱንም ለሀገሩ መስዋዕት በማድረግ የምግባር አርበኛ የሚሆን አለ፡፡ ሕዝብን በሰላም በመምራት በሕዝብ ልብ ውስጥ የሚነግስ የአገር መሪ ይኖራል፡፡ ጥቅሙን ሁሉ ለራሱ ሰብስቦ ወንድሙ የእሱ ለማኝ እንዲሆን የሚመኝና በዚህ ክፉ ሥራው የሚደሰትም አለ፡፡ ለዓለምና ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ የጥበብ ሥራዎችን የሚፈለስፉ ምሁራን አሉ፡፡ የሰው ልጅ በዚህ መልኩ ለልዩ ልዩ ዓይነት ተግባር የተፈጠረ መሆኑ ይታያል፡፡
የሰው ልጅ ከመቃብሩ አፈር በላይ የሚቀር ታሪካዊ ሥራ ሳይሰራ መቶ ዓመት ቢቀመጥ ትርፉ ምንድነው? ሰው ከዕድሉ ጋር እስኪናገኝ ግን በከንቱ መድከም አይኖርበትም፡፡ ጥረትና ድካም ከዕድል ጋር ሲገናኙ ምን እንደሚመስሉ “የሕልም ሩጫ” ብዬ በሰየምኩት መጽሐፍ ባሰፈርኩት ጽሑፍና በአንድነት ካቀረብኳቸው ፎቶግራፎች፣ ከእኔ ሕይወትና ሥራ መማር ይቻላል፡፡
* * *
የቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው የሕይወትና የሥራ ታሪክን የያዘው “የሕልም ሩጫ” መጽሐፍ በሁለት ሦስተኛ ገፆቹ የሰበሰባቸው ፎቶግራፎችም መረጃ ሰጪ ብቻ ሳይሆኑ ታሪክም ይናገራሉ፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ምኒልክ፣ የንግሥት ዘውዲቱና የእቴጌ ጣይቱ ምስሎችን ይዟል፡፡
የመጽሐፉ ባለታሪክ በልጅነታቸው በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ከነበሩትበት ዘመን አንስቶ በወጣትነት፣ በአርበኛነት፣ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎችና ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪያቸውን በተቀበሉበት ወቅት የተነሱትን ፎቶግራፎችንም አቅርቧል፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ በአልጋ ወራሽነት የስልጣን ዘመናቸው ከፈረንሳይ መንግስት የተሰጣቸው የ”ቪላ ካሚስትራ” ሕንፃ፤ አልጋ ወራሹ አውሮፓን ዞረው በጐበኙባቸው ወቅት የነበረው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ታሪክ የሚናገሩ ብዙ ፎቶዎችም አሉት፡፡
የባለታሪኩ ባለቤት ልዕልት የሻሽወርቅ ይልማ ላቋቋሙት የሕፃናት በጐ አድራጐት ድርጅት መርጃ ከሆኑትና 2ሺህ 800ብር ከተሸጡት ስዕሎች የተወሰኑት ፎቶግራፍ ተነስተው የመጽሐፉ አካል ሆነዋል፡፡ በዘይት ቀለም ቅብ ከሳሏቸው መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል፣ የጐንደር ግንብ፣ የምጽዋ ድልድይ…ስዕሎች ይገኙበታል፡፡ በ1930 ዓ.ም በኢየሩሳሌም የሳሉትና እግዚአብሔር አንዱን ዘመን እያጠፋ ሌላውን ሲያበራ የሚያሳየው ስዕል በተለየ ሁኔታ ያስደምማል፡፡
ረጲ አካባቢ ይገኝ በነበረው መኖሪያ ቤታቸው ግቢ “የዓለም መታሰቢያ” የሚል ሐውልት ያሰሩት ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው፤ መጽሐፋቸው ሊያስተላልፉ የፈለጉትን መልዕክት ቀደም ብለው በሐውልቱ ላይ ያመለከቱ ይመስላል፡፡ በሐውልቱ አንድ ሽማግሌ ዓለምን ተሸክሞ ይታያል፡፡
ዓለምን በሚወክለው የድንጋይ ሉል ላይ “ኃጢአት ሸክምሽ የከበደ፤ ሌቦችና ቀማኞች የሚካፈሉሽ ዓለም ሆይ!” የሚል ጥቅስ ተጽፏል፡፡ በመኖሪያ ቤታቸው አፄ ኃይለሥላሴን ጨምሮ የዩጐዝላቪያ መሪ የነበሩት ፕሬዘዳንት ቲቶን መሰል ታላላቅ ሰዎችን ያስተናግዱ እንደነበር የሚያሳዩ ፎቶግራፎችም አሉ፡፡
“ላንድ ሕዝብ ነፃነት ማግኘት ብቻ የሚበቃ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ተቀባዩ ሕዝብ የነፃነትን ትርጉም ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
ቮልቴር የሚባል የፈረንሳይ ሊቅ “ነፃነት ለሰው ሁሉ የሚገባው መብቱ ሲሆን የወገኑን ኑሮ ሳያበላሽና መብቱን ሳያስደፍር በጥንቃቄ እንዲሰራበት ያስፈልጋል’ ይላል፡፡” በማለት በአንድ ወቅት በቤተመንግሥት ተገኝተው ንግግር የደረጉት ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው፤ ከንባብ፣ ከትምህርትና ከሥራ ልምድ ያገኙትን ዕውቀት በተለያዩ መፃሕፍት እያዘጋጁ በማሳተም ይታወቁ ነበር፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 19 October 2013 12:38

ሰው ነው የረቀቀ

ሰው ነው የረቀቀ
ከሜርኩሪ ቬነስ፤ ከጨረቃ ከማርስ
ከፕሉቶ ኔፕቱን፤ ኡራኑስ የላቀ
ከጁፒተር ሳተርን፤ ከጣይ የደመቀ
ባካባቢው ሁሉ እያሸበረቀ፤
ሰው አደገ አወቀ፤
መሬት እንቁላሉን ሰበረ መጠቀ፤
ሰው ዓለምን አየ
በጨለማው ቦታ ዶቃ አንፀባራቂ
ውብ ሰማያዊ ኩዋስ፤ ሮዝ አብረቅራቂ፡፡
በተጣራው አየር በነጣው ደመና
ባረንጉዋዴው ባህር ውሃ ተሸፍና፤
ውብ ሉል ኮከብ አለም፤ የጠፈር ላይ ጤዛ፤
የሰው ልጆች እናት፤ የሰው ልጆች ቤዛ፡፡

የማታ ጀምበር
ካንዱ ቤት ወዳንዱ በጣራው ተራምዳ፤
የጋራውን እናት እየነካች ሄዳ፤
እዩት ከስር ጥላው፤
የማይደርስበትን፤
እዩት ሰውን ጥላው፤
ሲለፋ ሲባክን፡፡

Published in የግጥም ጥግ

             በአሜሪካዊ የሃይማኖት ሰባኪ እና ጥናታዊ ፊልም ሠሪ ጂም ራንኪን “ጂሰስ ኢን ኢትዮጵያ” በሚል ርእስ በአሜሪካ ውስጥ የታተመ መጽሐፍ ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም ተተርጉመው በአማርኛ ከቀረቡ መጽሐፎችም አንዱ ነው፡፡
ብዙ አንባቢዎች የትርጉም ሥራዎችን ያለማንበብ አቋም የያዙትን ምክንያት በሚገባ ማሳየት የሚችል ከመኾኑም በላይ፤ በሀገራችን መጽሐፍን የማሳተም ሥራን በያዙት ሰዎችም የሚፈፀመውን ጥፋት አጉልቶ የሚያሳይ የትርጉም ሥራ ነው፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ” በሚል ጯኺው ርእሱም ጭምር በብዙው ተገዝቶ ሳይነበብ አልቀረም፡፡ አሁንም በብር 40.00 እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ይህን መጽሐፍ የግድ መመልከት ያስፈለገበት ምክንያት ቢጠየቅ “የታለ“ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ የተባለው?” ለማለት ነው፡፡
አንድ አንባቢ በመጨረሻ ይህን ካልጠየቀ፣ ራንኪን በድፍረት የተናገረውን እና “ይኼ ነው ይህን የሚገልፀው ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ” ተብሎ የተጠቆመውን በመጻፉ ብቻ በቂ ነው ብሎ ተቀብሎታል ማለት ነው፡፡ አሊያም ደግሞ፣ ለአሜሪካዊው ፀሐፊ የመንፈስ መገለጥ ብቻ አሳምኖታል ማለትም ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል የቤተክርስትያን ሰባኪው ገና ከመነሻው ጀምሮ ሲገለጥለትና ሲገጣጠምበት የነበረውን የመንፈስ መገለጥ ምክንያት፣ ልክ ለራሱም እንደሆነለት አድርጐ በድፍኑ አምኖ ተቀብሎታል ከማለት ሌላ ምንም አይታሰብም፡፡
ራንኪንም ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ደርሶ እንደነበር ያሳመነው፣ በአስጐብኚው ተተርጉሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ የጣና ደሴት ገዳም ውስጥ እንደጸለየ የተነገረው እና ይሄንኑ ከሚተርከው ጥንታዊ ብራና ላይ በሞባይሉ ፎቶ ያነሳቸው የጥቂት መስመሮች ትርጉም ብቻ ይመስላል፡፡ በፎቶ ያነሳትን የግእዝ ጽሑፍ አሜሪካ ውስጥ ሊያገኛቸው ለቻሉት አንድ ካህን አሳይቶ በድፍኑ ልትተረጐምለት በቃች። በመጽሐፉ ላይ እንደጠቀሰው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ጋር ኢትዮጵያ ስለመግባቱ የሚናገር እንደሆነ ነው የነገሩት፡፡ እንግዲህ በነዚህ ብቻ ነው መግባቱን ራሱም ነው ከማለት ይልቅ በውስጣዊ መንፈሱ ሹክ እንደተባለም ሲገልፀው የነበረው፡፡ ምናልባት እሱ በቀጥታ ባይናገረው “የመንፈስ መገለጡ” ብቻ ሊሆን ይችላል ከማለት ውጭ በጭራሽ አይታሰብም፡፡
ራንኪን ኢየሱስ ከእናቱ ጋር ኢትዮጵያ መግባቱንና መቀመጡን እንዴት “ሊያውቅ” እንደቻለ የሚተርክባቸውን ገጾችና ሌሎች ተያያዥ የጉዞ ታሪኮችን እንመልከት፡፡
ጂም ራንኪን የቦብ ኮርኑክ አሣሽ ቡድን አባል ሆኖ ነው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የቻለው፡፡ቦብ ኮርኑክን እማናውቅ ካለን ወይም እማናስታውሰው ከሆነ፣ በኢትዮጵያ፣ አክሱም ውስጥ ታቦተ ሙሴ መኖር አለመኖሩን “በገዛ ራሴው መንገድ ላረጋግጥ” ብሎ የተነሳ ነበር፡፡ በአክሱም ጽዮን የነበረውን የቤክርስቲያን ቅርስ ጥበቃና ምዝገባ ኃላፊ ዲያቆንና ሌሎች ሁለት መነኮሳትን በረብጣ ዶላር ደልሎ፣ ጽላቱ በምሥጢር በሚቀመጥበት ገብተው እንዲመለከቱ የሞከረ ነበር፡፡ ሙከራው በሚያስደነግጥ አደጋ ተፈፀመ፡፡
ኮርኑክ ኤድዊን ፋውንዴሽን ሥራ አስኪያጅ ነው። ይህ ፋውንዴሽን የአክሱሙን እና ከዚህ በፊትም ትክክለኛዋ ሲና የት እንደነበረች ያሰሰ ድርጅት ነው፡፡
ፋውንዴሽኑ በአፖሎ ፕሮጀክት ጨረቃ ላይ በእግራቸው የቆሙና የተራመዱ ከተባሉት አንዱ የሆነው ኤድዊን፤ ከጨረቃ ጉዞው እንደተመለሰ የመሠረተው ድርጅት ነው፡፡ ጨረቃ ላይ እግሩን እንዳሳረፈ በኅዋው ውስጥ ሽቅብ አንጋጥጦ ይቺን ምድር ባያት ጊዜ “አንዲት በቀላሉ ፍርክስ የምትል ተሰባሪ ነገር” መስላ ታየችው፡፡ ወዲያውኑ ወደ ምድር ሲመለስ ምን ዓይነት ሥራ መሥራት እንዳለበት ወሰነ፤ ኤድዊን፡፡ ድሮ ከወላጆቹ ጋር ሳለ ሲያነብበው በነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉ ቦታዎችንና ቅርሶችን የማሰስና የመፈለግ ሥራ፣ ይህንንም የሚሠራ ድርጅት ማቋቋም፡፡ በዚሁ መሠረት ፋውንዴሽኑን መሥርቶ ሥራውን ሲጀምር፣ በተለይም ቀዳሚው ተፈላጊ አድርጐ ያሰበውን የኖኅ መርከብ ፍለጋውን ለማካሄድ ሲነሣ የሚረዳውን ሰው ፈለገ፡፡ ትላልቅ ተራሮች ላይ ተንጠላጥሎ መውጣትን እንዲያሰለጥነውና ለደህንቱም ጠባቂው እንዲሆን በማሰብ የኮሎራዶ ፖሊስ እና ወንጀል መርማሪ የነበረውን ይህንን መቶ አለቃ ኮርኑክን ቀጠረ፡፡ እያሰለጠነው ሳለ ግን የአሠሣው ሥራም ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ወሰነ፡፡
የኖኅ መርከብን ፍለጋው የቱርክ መንግሥት፣ አሳሾችን እንደ ሰላይ ቆጥሮ በማሰሩ ቀረ፡፡ ቀጣዩ ፕሮጀክት ሙሴ ጽላቶችን የተቀበለበት የሲናን ተራራ የት እንደሚገኝ መፈለግ ሆነ፡፡ በዚህም ላይ ኮርኑክ ከዋነኞቹ ፈላጊዎቹ አንዱ ነበር፡፡
የሲናን ፍለጋ ሥራው ካበቃ በኋላ የፋውንዴሽኑ ባለቤትና መሪ ኤድዊን ሞተ፡፡ ከዚህም የተነሳ ኮርኑክ የፋውንዴሽኑን ሥራ አስኪያጅነት ተረከበ። ታቦቱ የተሰጠበትን ሲናን እንዳገኟት፣ ያው ታቦት የት እንደደረሰ ማወቁ ደግሞ በኮርኒክ ታሰበ፡፡ እናም በቀጥታ ይገኝባታል ወደተባለችው ወደ ኢትዮጵያ ሊዘምት ተነሣ፡፡
ከዚህ በፊት እንዲሁ ስለታቦተ ሙሴ በአክሱም መገኘት፣ የታሪክ ፈለግን እየተከተለ በመመርመርና በማጥናት አክሱም ጽዮን በር ድረስ እያስረገጠ የተጓዘው ግርሃም ሃንኩክ ያቀረበውን ዘ ሳይን ኤንድ ዘ ሲል ኮርኑክ አንብቧል፡፡ “ግን አላረካኝም፣” ይል እና “ራሴ በራሴ መንገድ መፈለግ አለብኝ” ብሎ ይነሳል፡፡
ምናልባት ሃንኩክ የቃል ኪዳኑ ታቦትን ከርሱ በኋላ ለመፈለግ የሚነሳ ከመጣ፣ “እኔ ከደረስኩበት ላይ ተነስቶ አንድ ዕርምጃን ይራመድ፣” እንዳለው፣ እርሱ ከደረሰበት የሚቀጥለውን ርምጃ መራመዱ ነው ልንለው የምንችለው ዓይነት ጉዞ ነበር የተጓዘው፡፡ በገንዘብ ኃይል የመፈለግን መንገድ ነበር የመረጠው። ከዚህ ውጭ ያን ያህል የተሻለ የምርምርና የጥናት ሥራ አላደረገም፡፡
እንግዲህ፣ በዚህ ሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ ነበር የ”ኢየሱስ በኢትዮጵያ” ጸሓፊ ኮርኑክን ያወቀው። በዚሁ የአሠሣ ሥራው በአንዱ የአሜሪካ ቲቪ ለኮርኑክ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ዓይቶ ደወለለት፡፡ በመሰል ጉዳዮች ፍለጋና ዘጋቢ ፊልም በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጾ ይተዋወቃሉ፡፡
ኮርኑክ ለመጨረሻ ጊዜ የቃልኪዳን ታቦቱን ጉዳይ የሚፈጽምበትን ጉዞ ለማድረግ ሲነሳ ለጂም ራን ኪን ደውሎ፣ በዚያ ጉዞው ወደ ኢትዮጵያ ከሚጓዙት አንዱ እንዲሆን የመረጠው መሆኑን ነገረው፡፡ ሌሎች ከዚያ በፊት ይዟቸው ያልነበሩ ባለሞያዎችን ያካተተ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡
ይህ የኮርኑክ የመጨረሻ ጉዞ የፋውንዴሽኑ ባለቤት የኤድዊን መበለትም አብራ የመጣችበትና ለኢትዮጵያ መንግስት ፕሬዚዳንትም ጨረቃ ደርሳ ተመለሰች የተባለች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን በይፋ ማስረከብ የቻለችበት ነበር፡፡ (ያኔ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ ፕሬዚዳንቱ)
ለኮርኑክ የመጨረሻ በሆነው በዚህ ጉዞ፣ አክሱም ላይ ለአክሱም ጽዮን የቅርስ ምዝገባና ጥበቃ ኃላፊ ሆኖ የተሾመው ወጣት በተቀበለው ረብጣ ዶላር፣ ጽላቱ ወደሚቀመጥበት ቦታ መነኮሳት እንዲገቡና እንዲመለከቱ ቢያደርግም አልተሳካለትም፡፡ አንደኛው መነኩሴ ወዲያው ሲሞት ሌላው ደግሞ ሊሞት ሲያጣጥር ነበር የቀጠሮ ቀን ደርሶ ኮርኑክ ከነቡድኑ የገባው፡፡ ኮርኑክ የሚያጣጥረውን መነኩሴ ለማግኘት ተጣደፈ፡፡ አግኝቶ አነጋገረው፡፡ በኋላ ያም መነኩሴ ሞተ፡፡ ኮርኑክ የቃል ኪዳኑ ታቦት በአክሱም መኖሩን በዚህም አረጋግጦ ነበር፡፡ ቡድኑን ይዞ ለተጨማሪ ሥራ ወደ ጣና ሐይቅ ገዳሞችም ያመራው፡፡
ጣና ከመግባታቸው በፊት ወደ ቅማንቶች በመግባት ከአንዲት ቤተ እስራኤላዊት ድድ ዘሯን በክሮሞዞም የሚመረምሩበትን ናሙና ወስደዋል። በጣና ቂርቆስ ገዳም ውስጥ ከቤተክርስትያኑ ሕንፃ አጠገብ ከሚገኙ መቃብሮች የአንዱን አጽም በቁፋሮ ከፍተው፣ ከአጥንቱ ናሙና ለመውሰድም ጠይቀዋል፡፡ የኛን የተቀበሩትን ሰው ዘር የሚያውቁበትን ምርመራ ለማድረግ የፈለጉትን ናሙና ግን አላገኙም፡፡ በቦታው የዚያ ገዳም መሥራች እንደነበሩ የሚታወቁት መነኩሴ እንደተቀበሩበት ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ይህ አስቀያሚ ጥያቄአቸው በአበ ምኔቱ ሊፈቀድላቸው አልቻለም፡፡
አስጐብኚው ግን እንቢታቸውን እንዲያስለውጥላቸው በነገሩት መሠረት፣ አበ ምኔቱን አጥብቆ ይጠይቃቸዋል፡፡ አበ ምኔቱ በምንም ዓይነት እንደማይቻል በመግለፃቸው እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ቀረ፡፡
ከዚያ በጣና ቂርቆስ ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ቦታዎችና አለቶች ይጐበኛሉ፡፡ በርከት ካሉት የቡድኑ አባላት ፈንገጥ እያለ፣ መንፈሱ አንድ ነገር እንደጐደለ እና እንዲፈልግ እንደሚገፋፋው አድርጐ በሚያቀርበው ገለጻው ሣር ቅጠሉን እየጠራረገ፣ በአራት እግሩ እየዳኸ፣ በአንድ ቋጥኝ ጠፍጣፋ አናት ላይ ሲያነፈንፍ የነበረው ራንኪን፤ ሳያውቀው ከደሴቱ ጫፍ ደርሶ ዥው ብሎ ሐይቁ ውስጥ ሊወድቅ እንደነበረ ገልጿል፡፡ ለጥቂት የተረፈ መሆኑን ራሱው “ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ” ባለው መጽሐፉ ጽፎታል፡፡ ቋጥኙን ቧጥጦ ከሥር ውሃው ውስጥ የሚርመሰመሱት አዞዎች ቀለብ ከመሆን ዳነ፡፡
ሌሎቹ ጉብኝታቸውን ጨርሰው በመጨረሻ ከገዳሙ ከመውጣታቸው በፊት የሚያዩአቸውን ጥንታዊ ንዋያትና ቅርሶች በያዘች ያረጀች ትንሽዬ ታዛ ወርደው፣ መነኩሴው ቁልፍ ይዘውላቸው እስኪመጡ ቆመው ሲጠብቁ ጂም ራንኪን ወደ ኋላ ቀረ፡፡ አንዳች የቀረ ነገር እንዳለ ይሰማኛል” በማለት ያንን እንዲገልጽለት እዚያው ባገኘው ጠፍጣፋ ዓለት ላይ ተደፍቶ ይጸልይ ገባ፡፡
ከቤተክርስትያኑ መግቢያ አጠገብ ቆሞ እሱን ይጠብቀው ለነበረው ኢትዮጵያዊው አስጐብኚ አንድ ቄስ ይኼ ሰው የሚጸልይበት ላይ ኢየሱስም እዚህ ሳለ ይጸልይ እንደነበረ ነገረው፡፡ አስጐብኚው ይሄንኑ ለራንኪን ጮክ ብሎ ይነግረዋል፡፡ በቃ! ራንኪን የሚሆነውን ያጣል፡፡ የቀረው ነገር እንደሆነ ይሰማው የነበረውም ይኼው እንደነበረ ቅንጣት አልተጠራጠረም፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ገዳም ተቀምጦ ነው እርሱ በፀለየበት ዓለት ላይ ዘወትር “ከአባቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ይነጋገር የነበረው፡፡” እንዲያውም እሱ እንደገለጸው፤ “ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ መመርያን ይቀበል ነበር፡፡”
በዚህ ነገር ራንኪን በኃይለኛ ስሜት ውስጥ ገብቶ ሳለ፤ ይኼን በዝርዝር የሚናገረውን መጽሐፍ ደግሞ እታች እንደሚያገኙ አስጐብኚው በነገረው መሠረት ወደዚያው ተጣድፎ ይወርዳል፤ ሌሎቹ አባላቱ ቆመው በሚገኙበት፡፡
ካህኑ ይዘውት በመጡት መክፈቻ በከፈቷት ትንሽዬ ደሳሳ አሮጌ ቤት ውስጥ በኦሪት ዘመን መስዋዕት ይቀርብባቸው የነበሩ ንዋያት፣ ካህኑ ይለብሱት የነበረው፣ እንዲሁም ሁለት መለከቶችን ጭምር ያሳዩአቸዋል፡፡
አስቀድሞ ለጉብኝት ካናዳ ሄዶ በነበረበት ጊዜ፣ ከአንድ ጌጣጌጥ መደብር ለመገብየት ገብቶ ሳለ፣ ሻጭቱ “ለአንተ የሚሆን ልዩ ዕቃ ና ላሳይህ” ብላ ወደ ሌላ ክፍል ወስዳው ከብር የተሰራ የእሥራኤላውያን ቀንደ መለከት ሥል የተንጠለጠለበት ጌጥ፣ ከታቦቱ ጋር የማይጠፋ እንደነበር ገልጻለት፣ እንዲገዛ አድርጋው ነበር፡፡
ጂም ራንኪን በዚህ የጌጣጌጥ መደብር ውስጥ ይህን ከገዛበት ዕለት በፊት በነበረው ሌሊት ነው በእንቅልፉ ውስጥ ሳለ፣ የቃልኪዳኑን ታቦት ለምን እንደማይፈልገው የተጠየቀው፤ እሱ እንደተረከው። ደንግጦ ባነነ፣ ያ ጥያቄ ሲያስጨንቀው ቆየ፡፡ ጧት ተነሳ፣ ከውሎው ተመልሶ ጌጣጌጥ ሊገበይ በገባበት ነበር፣ ያ የቀንደ መለከቱን የብር ጌጥ የገዛው፡፡ በጣና ቂርቆስ ገዳም ከነዚያ ንዋያት በተጨማሪ ኢየሱስ ከእናቱ ጋር እዚያ እንደተቀመጠ የሚተርከውን መጽሐፍም አሳዩአቸው፡፡ ራንኪን ጥቂት ገጾችን ፎቶ አነሳ፡፡
በዚሁ የኢትዮጵያ ቆይታቸው አብቅቶ አሜሪካ ሲገቡ፣ ያን በፎቶ የያዙትን የግእዝ ቃል ተርጓሚ ፈለጉ፡፡ ያገኟቸው ኢትዮጵያዊ ቄስ አስቀድሞ እንደተገለፀው ያንኑ ታሪክ የሚናገር መሆኑን ገለፁለት፡፡
አበቃ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ የቱ ጋ ነው ያለው?
ይሄን ሾላ በድፍን የተወበትን መጽሐፍ ነው “ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ” ሲል የሰየመው። መጽሐፉ ከዚህ ይልቅ ሌሎች ዓላማዎች የያዘ ይመስላል፡፡ በአክሱምና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ወንጌልን የመስበክ ፕሮጀክት አብረው ከተጓዙት ጋር ሲነድፉ ይገኛሉ፡፡ ከሁሉ ሁሉ የሚያስገርመው ግን ኢትዮጵያውያንን ለመስደብ እና ለመንቀፍ የመቸኮሉ ነገር ነው፡፡ በስንቱ መጽሐፍ ተጽፎ፣ በየጊዜው እየተገለፀ የሚገኘውን ይህን ጉዳይ፣ “ለምንድነው የሚደብቁት” እያለ በተደጋጋሚ ይቆጣል፡፡
ይሄም ሳያንሰው እግዚአብሔር እንዴት “በዚች ውኃዎቿ ሁሉ በበሽታ የተበከለ…” አገር የቃል ኪዳን ታቦቱን የመሰለውን ሊደብቅባት ቻለ? በማለት ሕዝቡንና ሀገሪቱን ይሰድባል፡፡
ምናልባት የዚህ መጽሐፍ አንድ ጥቅም ተደርጐ ሊወሰድ የሚችለው፣ ፀሐፊው በደርዘን ፓንቶችና ካልሲዎች ሳይቀር ወሻሽቆ በሻንጣው ደብቆ ያወጣቸውን ዓይነቶች የቅርሶች ዝርፊያ እንደሚፈፀም እና ጥበቃው ምን ያህል ልል እንደሆነ ማሳየቱ ብቻ ይመስለኛል፡፡
ሌሎች መፅሃፉን ያነበቡ ሰዎች ግን “ቢያንስ ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ” እንደነበረ መገለጹን እንደ አንድ ጥቅም ቆጥረውታል፡፡
ግና የታለና እሱ?

 

Published in ጥበብ
Page 5 of 16