ብቸኛዋ ኩባዊት ባለሙያ የስራ ውላቸውን ጨርሰዋል
ሆስፒታሉ አስከሬን አልቀበልም ብሎ ማስታወቂያ ለጥፏል

በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ስር በሚገኘው የአገሪቱ ብቸኛ የአስክሬን ምርመራ ክፍል ሲሰሩ የቆዩ ኩባዊት የህክምና ባለሙያ የስራ ውላቸዉን አጠናቅቀው ስለተሰናበቱ የምርመራ አገልግሎቱ ተቋረጠ፡፡ ለስድስት አመት የስራ ውል እየተፈራረመ በሚያስመጣቸው ኩባዊ ባለሙያዎች አማካኝነት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የአስክሬን ምርመራ ክፍል፣ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ሲያገለግሉ ከቆዩት ኩባዊት ዶክተር ጋር የተፈራረመው ውል ለሁለት አመት ብቻ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በወቅቱም፣ በአስከሬን ምርመራ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ሃኪሞች ባለመኖራቸው ከኩባ ተጨማሪ ባለሙያዎችን ለማስመጣት አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቅቄያለሁ በማለት አንድ የሆስፒታሉ የስራ ሃላፊ መናገራቸዉ ይታወሳል፡፡ የኩባዊቷ ሃኪም የወር ደሞዝ 6ሺ ብር እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከሦስት ሳምንት በፊት መስከረም 6 ቀን 2006 ዓ.ም ባለሙያዋ በመታመማቸው ለሶስት ቀናት የአስከሬን ምርመራ ተቋርጦ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በርካታ የሟች ቤተሰቦችና ሃዘንተኞች ለቀብር ስነ ስርዓት መንገላታቸውን እንደዘገብን ይታወቃል። ይሁን እንጂ፣ ኩባዊቷ ሃኪም የስራ ውላቸዉ ተጠናቅቆ ሰሞኑን ሲሰናበቱ ምትክ ባለሙያ ባለመዘጋጀቱ አገልግሎቱ የተቋረጠ ሲሆን፣ ሆስፒታሉ ለምርመራ የሚመጡ አስከሬኖችን እንደማይቀበል የሚገልፅ ማስታወቂያ ለጥፏል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምርመራ ሊካሄድባቸዉ የሚገቡ አስከሬኖችን ለማስቀመጥ የሚያስችል የማቆያ ስፍራ ስለሌለው በሆስፒታሉ ውሳኔ አልተስማማም፡፡ የፖሊስና የሆስፒታሉ ሃላፊዎች ተነጋግረውም ነው፣ ሆስፒታሉ ትናንት አስከሬኖችን መቀበል የጀመረው። ሆስፒታሉ መቼ የምርመራ ባለሙያ እንደሚያገኝና መቼ አገልግሎቱን እንደሚጀምር የታወቀ ነገር የለም፡፡

Published in ዜና

            የዩኒቨርስቲ የምዝገባ ቀን እንዳያመልጣቸው የሰጉ ተማሪዎች ሰሞኑን ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ የአውቶቡስ ትኬት ለመቁረጥ እየጣሩ መሆናቸውን ገልፀው፤ የትራንስፖርት ታሪፍ በግማሽ ተጨምሮበትም ትኬት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
ወደ ጅማ ለመሄድ የ177 ብሩ ትኬት ሃምሳ በመቶ ተጨምሮበት ከ260 ብር በላይ ሆኖበት የተቸገረ ተማሪ፤ ያም ሆኖ ትኬት አልቋል በሚል እንደተንገላታ ገልጿል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ በኩል ወደየተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ለመሄድ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ተማሪዎች፤ ባልተጠበቀ የታሪፍ ጭማሪና በትኬት እጦት እንደተንገላቱ ገልፀዋል፡፡
በአዲስ አበባ የአውቶቡስ መነሃሪያ የትራንስፖርት ስምሪት ተቆጣጣሪ በበኩላቸው፤ የትራንስፖርት እጥረት የተፈጠረው ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በተመሳሳይ ቀናት ተማሪዎችን ለምዝገባ በመጥራታቸው ነው ብለዋል፡፡
በየማለዳው ወደ አውቶቡስ መናሃሪያ ሲመላለስ ከሰነበቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው ሰላማዊት ይፍሩ፣ የአርባ ምንጭ ትኬት ለመቁረጥ ከሌሊቱ 10 ነው አውቶቡስ ተራ የደረሰችው፤ ትኬት ሻጮች በቢሯቸው አልነበሩም፡፡ እስከ ረፋድ 3 ሰዓት ድረስ ብትጠብቅም ትኬት ሻጮች ከነአካቴው ባለመምጣታቸው ግራ እንደገባት ተናግራለች፡፡ ዲላ ዩኒቨርስቲ የተመደበ ሌላኛው ተማሪም፣ ማክሰኞ እለት ለሁለተኛ ቀን ቲኬት ለማግኘት በሌሊት መጥቶ አልተሳካለትም፡፡ ሰኞ እለት መናሃሪያው ውስጥ ለወረፋ ከተሰለፉ ተማሪዎች አንዱ እንደነበረ ገልፆ፣ አንድም ቲኬት ሳይሸጥ፣ አንድም ተማሪ ትኬት ሳይቆርጥ የመደበኛ ቲኬት አልቋል እንደተባለ ገልጿል፡፡ የፈለገ በ”ፐርሰንት” የሚሸጠውን ትኬት መግዛት ይችላል” ተብሎ እንደተነገራቸው ጠቅሶ፣ አቅም ያላቸው የተወሰኑ ሰዎች በመደበኛ ታሪፍ ላይ ግማሽ ያህል ጨምረው እየከፈሉ ትኬት እንደቆረጡ ተናግሯል፡፡ በጭማሪ ክፍያ የሚቆረጠው ትኬትም ቢሆን ወዲያው “አልቋል” ተብሎ ተቋርጧል፡፡ ነገር ግን ከመነሃሪያው ቅጥር ግቢ ውጭ የ50 ብር ጭማሪ እየተደረገባቸው ትኬቶች እንደሚሸጡ ይገልፃል - ወደ ዲላ ለመሄድ የተቸገረው ተማሪ፡፡
ቀድሞ መኪና ሲያመልጥ ወይም ሲበላሽ ቲኬቱን መልሶ ገንዘብ መቀበል እንደሚቻል የሚገልፁት ተጠቃሚዎች፤ አሁን ግን መደበኛው ታሪፍ እንጂ 50 በመቶ (የፐርሠንት) ጭማሪው እንደማይመለስ ገልፀዋል፡፡
ከተለያዩ ክልሎች በአዲስ አበባ በኩል ወደየተመደቡበት ዩኒቨርስቲ የሚጓዙ ተማሪዎች ይበልጥ ተቸግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተመድቦ እሁድ ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ የመጣ የደብረ ብርሃን ተማሪ፤ ሠኞ እለት ወደ አርባ ምንጭ እሄዳለሁ የሚል ተስፋ የነበረው ቢሆንም፤ በማግስቱም ትኬት ስላላገኘ የምዝገባ ቀን እንዳያልፍበት መስጋቱን ተናግሯል፡፡
ብዙ መንገደኞች እየተጉላሉ መሆናቸውን ያመኑት የመነሃሪያው የህዝብ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ አቶ ሃይሌ ገብሬ፤ የመነሃሪያው አስተዳደር ሃላፊዎችና ሠራተኞች በተቻላቸው አቅም ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ የትራንስፖርት እጥረት የተፈጠረው ዩኒቨርስቲዎች በተመሣሣይ ጊዜ ተማሪዎቻቸውን በመጥራታቸው ነው የሚሉት አቶ ሃይሌ፤ በቲኬት አቆራረጥ ላይ ለሚነሱ ቅሬታዎች ተጨባጭ ማስረጃ እንዳልቀረበላቸው ገልፀዋል፡፡ ከሌሊቱ 10፡30 ጀምሮ መነሃሪያው እንደሚከፈትና የቲኬት ቢሮዎችም (ፉካዎች) ደንበኞቻቸውን እንደሚያስተናግዱ የገለፁት አቶ ሃይሌ፤ ቲኬት ቆራጮች የትራንስፖርት ቢሮው ሠራተኞች ሣይሆኑ በመነሃሪያው ውስጥ ያሉት ከ20 በላይ የትራንስፖርት አገልገሎት ሠጪ ማህበራት ሠራተኞች ናቸው ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ምዝገባ ሲቃረብና በበአል ወቅቶች የተጓዦች ቁጥር ስለሚጨምር የቲኬት መቁረጫ ቢሮዎቹ እየተጣበቡ ከቢሮ ውጭ ቲኬት ለመቁረጥ ይገደዳሉ የሚሉት አቶ ሃይሌ፤ “በዚህ መሃል አልፎ አልፎ ህገወጥ ተግባራት ሊፈፀሙ ይችላሉ” ብለዋል፡፡ የመነሃሪያው አስተዳደር በውስን የቁጥጥር ሠራተኞች በተቻለው አቅም ቁጥጥር ያካሂዳል፤ ከመነሃሪያው ውጪ ትኬት ይቆረጣል የሚባለው ቅሬታ ግን፣ በአካል ሳናይ ወይም ተጨባጭ ማስረጃ ሳይቀርብልን የትራንስፖርት ማህበራት ሠራተኞችን ጥፋተኛ ማድረግ አንችልም” ብለዋል፡፡
የ“ፐርሠንት ጭማሪ” የሚባለው ክፍያ ምን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ሃይሌ፤ በአንድ መስመር የሚመደቡት አውቶብሶች በቂ በማይሆኑበት ጊዜ ተጨማሪ አውቶቡሶች በጊዜያዊነት እንዲመደቡ የሚደረግበት አሠራር እንደሆነ ጠቁመው፣ በጊዜያዊነት የተመደቡ አውቶቡሶች ተሣፋሪውን አድርሠው ባዶአቸውን ስለሚመለሱ ቢያንስ የነዳጅ ወጪ ለመሸፈን በመደበኛው ታሪፍ ላይ ማካካሻ ክፍያ ይጨመርበታል ብለዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ከ400 ኪ.ሜ በላይ ለሚርቁ ቦታዎች 35 በመቶ፣ ከዚያ ለሚያንሡት ደግሞ 50 በመቶ ጭማሪ ይደረጋል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ቲኬት የሚመልሱ ደንበኞች ከከፈሉበት መደበኛ እና ጭማሪ ታሪፍ ላይ 10 በመቶ ተቀናሽ ተደርጐ ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸው አቶ ሃይሌ ጠቅሰው፤ 10 በመቶ የሚቀነሠውም መኪናው ነዳጅ አቃጥሎ በተቆረጠ ቲኬት ስለሚጓዝ ነው ብለዋል፡፡

 

Published in ዜና
  • ሁለት ዓመት የሚፈጀው የባቡር ፕሮጀክት ችግሩን በከፊል ይፈታል ተብሏል 
  • የመንግስት ሠራተኞች በቅርቡ ሰርቪስ ይመደብላቸዋል

በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለው በቅርቡ ነው፡፡ የትራንስፖርት ተገልጋዩ ግን በየቀኑ እየተሰለፈበት ነው - ታክሲ ጥበቃ፡፡ አንደኛው ረጅም ሠልፍ ውስጥ የታክሲ ወረፋ ይዞ ያገኘሁት ወጣት ዳንኤል መዝገቡ፤ ከቃሊቲ መኖርያ ቤቱ 4 ኪሎ ወደሚገኘው መስሪያ ቤቱ ለመድረስ ከ3 ሠአት በላይ እንደሚፈጅበት ይናገራል፡፡
“ጠዋት ጠዋት ሁሌ ስለማረፍድ ከአለቆቼ ጋር ጭቅጭቅ ነው፣ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያም ደርሶኛል” የሚለው ዳንኤል፤ “ሠአታትን በሚወስደው የጠዋት ጉዞ አካሌ ተዳክሞና ዝሎ ቢሮ ስለምደርስ ስራዬን በአግባቡ መወጣት አልችልም” ይላል - በትራንስፖርት እጥረት የደረሰበትን ሲናገር።
ጠዋት እና ማታ ታክሲዎች ሆን ብለው ከመስመራቸው ይጠፋሉ ያለኝ ደግሞ ሌላው የትራንስፖርት ተጠቃሚ ተመስገን ይህደጐ ነው፡፡ “ሠልፍ ሲያዩም የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ፤ አማራጭ አጥቶ የቆየው ተጠቃሚም ያለማንገራገር የተጠየቀውን ከፍሎ ይጓዛል” ብሏል ተመስገን፡፡
የትራንስፖርት ቁጥጥር ሠራተኞች ይሄን እያዩ በቸልታ ያልፉታል የሚለው ተመስገን፤ ህብረተሰቡ በዚህ መሃል እየተበዘበዘ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከጦር ሃይሎች ሃያ ሁለት እየተመላለሰ እንደሚሠራ የነገረኝ አንድ ወጣት በበኩሉ፤ በመስመሩ ላይ የተመደቡ ታክሲዎች እያቆራረጡ ስለሚጭኑ ከገንዘብ፣ ከጊዜ አጠቃቀምና ከጉልበት አንፃር በርካታ ኪሣራዎች እንደሚያጋጥሙት ይገልፃል፡፡
ተገልጋዮች የትራንስፖርት ዘርፉ ችግር በማለት የሚጠቅሷቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ የታክሲዎች እያቆራረጡ መጫን፣ ከታሪፍ ውጪ ማስከፈል፣ በቀጠናቸዉ አለመስራት፣ የመንገድ መዘጋጋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይ ከባቡር ግንባታው ጋር በተያያዘ መንገዶች በሚዘጋጉባቸው መስመሮች አላግባብ የታሪፍ ጭማሪ ይደረጋል፡፡ ለምሣሌ ከስታዲየም እስከ ቃሊቲ መነሐሪያ 7 ብር ከ50 የነበረው ታሪፍ፤ አሁን እስከ 10 ብር እየተጠየቀ ነው፡፡ አልከፍልም ያለ ተሣፋሪ ከመውረድ ውጭ አማራጭ የለውም፡፡
በመገናኛ ዞን ፀሃይ የባለታክሲዎች ማህበራት ሊቀመንበር አቶ አበባው ካሣ፤ በአሁን ሠአት ተገልጋዩም አገልጋዩም በእኩል እየተጐዱና ብዙ ተግዳሮቶች እየተጋፈጡ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአራቱም የከተማይቱ ማዕዘናት እየተገነባ ካለው የባቡር መንገድ ጋር ተያይዞ የመንገዶች መዘጋጋት ዋና ችግር እንደሆነ ያሠምሩበታል፡፡
በዚህ ሳቢያ የታክሲያችን ምልልስ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል የሚሉት አቶ አበባው፤ ቀድሞውኑ ያሉት ተሽከርካሪዎች ውስን ሆነው ሣለ የምልልስ መጠናቸው እንዲቀንስ መገደዱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል ይላሉ፡፡
አንዳንድ የታክሲ አሽከርካሪዎችም በማህበራቱ የሚነሱትን ችግሮች ይጋሩታል፡፡ ስሙ እንዲገለጽ ያልፈቀደ ከጦር ሃይሎች 22 መስመር የሚሠራ አንድ ታክሲ አሽከርካሪ፤ የሚነዳት ታክሲ በናፍጣ ስለምትሰራ ለባለቤቶቹ በቀን 350 ብር ገቢ ማድረግ የሚጠበቅበት ቢሆንም በመንገዶች መዘጋጋት የተነሳ ያን ያህል ገቢ ለማግኘት እንደሚቸገርና ከባለንብረቶች ጋር ሁሌ እንደሚነታረክ ይገልፃል። ባሳለፍነው ዓመት የመጨረሻ አራት ወራት ውስጥ ብቻ አራት ሚኒባስ ታክሲዎችን ቀያይሯል - ከባለቤቶቹ ጋር ባለመግባባት፡፡
በሐምሌ ወር አጋማሽ በቤንዚን የምትሠራ ሚኒባስ ማሽከርከር ጀምሬ ነበር የሚለው ወጣቱ፤ ለባለቤቶቹ በቀን 290 ብር ገቢ ማድረግ የሚጠበቅበት ቢሆንም አንዳንዴ በመንገድ መዘጋጋት የቢያጆ (ምልልስ) መጠን ስለሚቀንስ በገቢ ጉዳይ ላይ አለመግባባቶች ይፈጠሩ ነበር ይላል፡፡ በአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት ኮርፖሬሽን ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ወጋየሁ አሰፋ፤ በከተማዋ ለተፈጠረው የትራንስፖርት ችግር በግንባታ ላይ ያለውን የባቡር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ተጠያቂ ያደርጋሉ። የአስፓልት መንገድ ግንባታዎች በ2006 ዓ.ም በየአካባቢው ተጠናክረው መቀጠላቸውም የችግሩ መንስኤዎች ናቸው - እንደ ኃላፊው፡፡ እነዚህ እስከሚጠናቀቁ ለሁለት አመታት ችግሩ ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ሃላፊው ይገልፃሉ፡፡
ሃላፊው እንደሚሉት፤ በ2007 ይጠናቀቃል ተብሎ ከሚጠበቀው የባቡር መስመር በተጨማሪ የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት የሚጀምርበት ሁኔታ በጥናት ላይ ነው፡፡ ባቡሩ ሙሉ ለሙሉ ወደ አገልግሎት ሲገባ የከተማዋን 25 በመቶ የትራንስፖርት ችግር የሚያቃልል ሲሆን ሌላው በሚኒባስ፣ በአውቶቡስ እና በሌሎች አማራጮች የሚሸፈን ይሆናል፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ግን በአጭር መፍትሔነት የተያዙ አማራጮች አሉ፡፡ አንደኛው በ2006 ዓ.ም የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎትን አጠናክሮ ማስቀጠል ነው፡፡ ለዚህም ሲባል 150 አዳዲስ የአንበሳ አውቶቡሶች በያዝነው አመት ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ የሚደረግ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 50 የሚሆኑት በሚቀጥለው ሣምንት ስራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች በስራ መግቢያና መውጫ ሰአት ሠርቪስ የሚሰጡ 410 የሚሆኑ አውቶቡሶች ለመግዛት ታስቧል የሚሉት አቶ ወጋየሁ፤ እነዚህ የአመቱ አጋማሽ ላይ ወደ ስራ የሚገቡ ከሆነ የመንግስት ሠራተኛውን ከማመላለስ ባሻገር ለህዝቡም በተመጣጣኝ ዋጋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡
ህብረተሰቡ በስፋት ቅሬታ የሚያቀርብባቸው የሚኒባሶች አቆራርጦ መጫን፣ መስመር ላይ አለመገኘት እና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል የመሳሰሉትን ለማስቀረትም በየክፍለ ከተማው የተለያዩ ኮማንድ ፖስቶችን በማቋቋም ጠንከር ያለ ቁጥጥር ለማድረግ መታሰቡን ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
የችግሩ የመጨረሻ መፍትሔ፤ በየደረጃው የሚወሰዱ የማቃለያ የመፍትሔ እርምጃዎችን መጠባበቅ እና ሰፊ ተስፋ የተጣለባቸውን በአማካይ ሁለት አመት የሚፈጀውን የባቡር ፕሮጀክት ጨምሮ አዳዲስ መንገዶች እስኪጠናቀቁ መጠባበቅ መሆኑን ከሃላፊው ገለፃ መረዳት ይቻላል፡፡

Published in ዜና

                ከዛጒዌ ስመ ጥር ነገሥታት አንዱ በነበሩት በንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ ዘመነ መንግሥት ከተሠሩት ኪነ ሕንጻዎች አንዱ የኾነው ይምርሐነ ክርስቶስ፤ የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ የ2014 ተተኳሪ መካነ ቅርስ (2014 World Monuments Watch) ሆኖ ተመረጠ፡፡
ፈንዱ መስከረም 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ዋና ጽ/ቤቱ በሚገኝበት በኒው ዮርክ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው÷ እ.አ.አ በ2014 ዓለም በትኩረት ሊያውቃቸው፣ ሊጠብቃቸውና ለትውልድ ሊያስተላለፍላቸው ይገባል ካላቸው የ41 አገሮች ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ልዩ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚታይበት የይምርሐነ ክርስቶስ መካነ ቅርስ አንዱ ኾኖ መመረጡ ተገልጧል፡፡
“ወርልድ ሞኑመንትስ ዎች” በተሰኘው ፕሮግራሙ ለአደጋ የተጋለጡና ዝነኛ የቱሪስት መስሕብ የኾኑ ታሪካዊ ኪነ ሕንፃዎችንና ባህላዊ መካነ ቅርሶችን በማስተዋወቅ፣ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ በመለገሥ ዘመን ተሻጋሪ እንዲኾኑ ዓለም አቀፍ ቅስቀሳ የሚያደርገው ወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ፣ በዝርዝሩ ያካተታቸው የተመረጡ ቅርሶች ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙና በአግባቡ እንዲጠበቁ በዓለም ዙሪያ ያሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በዩኔስኮ የተመዘገቡ በርካታ የዓለም ቅርሶች የፈንዱ ተጠቃሚ ሲኾኑ ከእኒህም መካከል ፈንዱ እ.ኤ.አ በ1966 ሲቋቋም የክብካቤና ድጋፍ ሥራውን የጀመረባቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ መቅደስ እንደሚገኙበት በመግለጫው ተመልክቷል።
የይምርሐነ ክርስቶስ መካነ ቅርስ በዓለም አቀፍ ፈንዱ ተመራጭ እንዲኾን በመጠቆምና ለምርጫው የሚያግዙ መረጃዎችን በማቅረብ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ለአዲስ አድማስ የገለጸው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ክብካቤና ልማት ማኅበር፤ መካነ ቅርሱ የ2014 የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ ተመራጭ መኾኑ ኪነ ሕንጻውን የበለጠ ለማስተዋወቅና ለማልማት ዕድል ይሰጣል ብሏል፡፡ ቅርሶች ዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ያበረክቱ ዘንድ ራእይ የሰነቀው ሀገር በቀል ማኅበሩን ጨምሮ በቅርስ ክብካቤ ዙሪያ የሚሠሩ ባለሞያዎች፣ የሥራ ሓላፊዎችና ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የብዙኀን መገናኛና ሌሎች አካላት ጋራ በመተባበር እንንዲንቀሳቀሱም ምቹ ኹኔታ ይፈጥራል ተብሏል፡
ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት በሰሜን ወሎ ወግረ ስኂን በሚባል ቦታ ሰፊና ግርማ ሞገስ ባለው የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ በውኃ ላይ እንደታነፀ የሚታመነውና ልዩ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይበት ይምርሐ ክርስቶስ÷ በአገራችን ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረውን የቤተ መንግሥት ሕንጻ፣ በድንቅ ጥንታዊ ሥዕሎችና ንድፎች ያሸበረቀ ቤተ መቅደስ አሰናኝቶ የያዘ መካነ ቅርስ ነው፡፡ በተጨማሪም ልዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች፣ ያልፈረሱና ዕድሜ ጠገብ የሰው ዐፅሞች፣ የሀገር በቀል ዕፀዋት ጥቅጥቅ ደንና ማራኪ መልክአ ምድር የሚገኙበት ነው፡፡

 

Published in ዜና

በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ “በደቡብ ክልል ሶስት ምክትል ርዕሳነ መስተዳድሮች ከስልጣናቸው ተነሱ” በሚል ከወጣው ዘገባ ጋር ተያይዞ ከአዲስ አበባ ወደ አዋሳ ተወስዶ ለአንድ ቀን የታሰረው የሪፖርተር አዘጋጅ (ማኔጂንግ ኤዲተር) መላኩ ደምሴ፤ ትላንት ተለቆ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡
ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ሶስት ሰዎች “በተጠረጠሩበት ወንጀል ይፈለጋሉ” የሚል መጥሪያ በመስጠት አዘጋጁን ከቢሮው እንደወሰዱትና እንደታሰረ የተገለፀ ሲሆን፤ ትላንት ጠዋት ፍ/ቤት ይቀርባል ተብሎ ቢጠበቅም “ዳኞች አልተሟሉም፤ ስንፈልግህ እንጠራሃለን” ተብሎ መለቀቁ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

            በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እና በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የኤምባሲና የቆንፅላ ፅ/ቤት አገልግሎቶችን ለማግኘት የሕዳሴ ግድብ ቦንድ እንድንገዛ እየተገደድን ነው አሉ፡፡ “ሁሉም ስደተኛ ተሰብስቦ ያሳለፈው ውሳኔ ስለሆነ የግድ ቦንድ መግዛት አለባችሁ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ስደተኞቹ ተናግረዋል፡፡ በአባይ ወንዝ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተስማማበት ፕሮጀክት እንደመሆኑ፣ እኛም ድጋፋችንን በተለያየ መንገድ በመስጠት ላይ ነን የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የገንዘብ መዋጮውና የቦንድ ግዢው የግዴታ መሆኑን ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

የቦንድ ግዢም ሆነ መዋጮ በዜጎች ፈቃደኝነት የሚፈፀም እንደሆነ መንግስት በተደጋጋሚ እየገለፀ መመሪያ ሲያስተላልፍ እንደነበር ያስታወሡት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ይሁን እንጂ በዱባይ እና በሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲዎች ወይም የቆንፅላ ፅ/ቤቶች ግን ፓስፖርት ለማሣደስና ሌሎች አገልግሎቶች ለማግኘት ስንሄድ፣ ቦንድ እንድንገዛ እንገደዳለን ብለዋል፡፡ ለ10 አመታት ከሚኖርበት ከሳዑዲ አረቢያ ባለፈው ሣምንት ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን የሚናገረው ጀማል አረቦ ኢስማኤል፤ ቢያንስ በ500 ሪያል (ወደ 3ሺ ብር ገደማ) ቦንድ መግዛት አለብህ እንደተባለ ገልጿል፡፡ ቅሬታቸውን ለኤምባሲዎችና ለቆንስላ ፅ/ቤቶቹ አቅርበው እንደሆነ ተጠይቆ ጀማል ሲመልስ፤ ብዙ ስደተኞች በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ጠቅሶ፣ መፍትሄ ግን አልተሰጠንም ብሏል፡፡

“ቃል ስለገባችሁ በቃላችሁ መሠረት የቦንድ ግዢውን ፈፅሙ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አቶ ጀማል ገልጿል፡፡ የቦንድ ግዢ በእያንዳንዱ ሰው ፈቃደኝነትና ውሳኔ እንጂ፣ የተወሰኑ ሰዎች ተሰብስበው ወስነዋል ተብሎ በሁሉም ሰው ላይ ግዴት የሚጫን መሆን የለበትም ብሏል - ጀማል፡፡ “ስንቸገር ዞር ብሎ ያላየንና በችግራችን ጊዜ ያልደረሠልን ኤምባሲ፤ የዜጐችን የላብ ውጤት በአስገዳጅ ሁኔታ መቀማቱ ተገቢ አይደለም” የሚለው ጀማል፤ ሁሉም ነገር በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ይላል፡፡ በሳዑዲ አረቢያ ለ6 አመት የኖረው ሌላው ወጣት በበኩሉ፣ በርካቶች ለቦንድ ግዢ የሚጠየቁትን ክፍያ በመሸሽ ወደ ኤምባሲው አገልግሎት ለማግኘት መሄድ እንደማይፈልጉ ተናግሯል፡፡

“እያንዳንዱ ዜጋ ቦንድ ግዢውን በፍቃደኝነት ብቻ ነው የሚሣተፈው፤ በምንም ሁኔታ አይገደድም” የሚለውን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ቃል አስታውሶ፣ አሁን ግን ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ብሏል፡፡ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ በዱባይ የምትኖር ሌላዋ አንዲት ወጣት፤ ፓስፖርት ለማሣደስ ወደ ቆንፃላ ፅ/ቤቱ ብታመራም 1000 ድርሃም ካልከፈልሽ አገልግሎት ማግኘት አትችይም መባሏን ገልፃለች። 500 ድርሃም ለቦንድ ግዢ ሲከፈል ቀሪው 500 ደግሞ ይህን ጉዳይ ለማስፈፀም ለተቋቋመው ኮሚቴ ተብሎ ይከፈላል የምትለው ኢትዮጵያዊቷ፤ ክፍያው ካልተፈፀመ ከማንኛውም የቆንስላ ፅ/ቤት አገልግሎት ማግኘት አይቻልም ብላለች፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ በስልክ አግኝተን ያነጋገርናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሣደር ዲና ሙፍቲ፤ “ይሄ ስለመፈፀሙ የተጨበጠ መረጃ የለንም፣ ነገር ግን ማስገደድ ተቀባይነት የሌለውና ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡ ተገቢ እንዳልሆነ ከዚህ በፊትም ተነግሯል” ብለዋል፡፡ አክለውም “ይሄ ድርጊት ተፈፀመብን የሚሉም ጥቆማውን ለመስሪያ ቤታችን ማሣወቅ ይችላሉ” ብለዋል፡፡

Published in ዜና

                       ኢትዮጵያና ናይጀርያ ከሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚያደርጉት የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታ በከፍተኛ ደረጃ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ዋልያዎቹ ብራዚል በምታዘጋጀው 20ኛው የዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ ሲያነጣጥሩ ንስሮቹ አምስተኛ ተሳትፏቸውን አቅደዋል፡፡ ሱፕር ስፖርት ከትናንት በስቲያ በሰራው ዘገባ ዋልያዎቹ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት ናይጄርያን ለማንበርከክ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡ ሙሉ ዝግጅቱን ነገ የሚጀምረው የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን በተለይ የአዲስ አበባ የአየር ሁኔታ ሊደርስ በሚችለው ጫና ተጨናንቆ ሰንብቷል፡፡

የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ለመምራት አራት ካሜሮናዊያን ዳኞች መመደባቸውን የገለፀው ፊፋ ፤የጨዋታው ኮሚሽነር ከዚምባቡዌ እንዲሁም በፊፋ ታዛቢነት የሚሰሩ ስዊዘርላንዳዊ እንደሆኑ የሴካፋ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ የሆኑት ኬንያዊው ኒኮላስ ሙንሶኜ በሴክሩቲ ኦፊሰርነት መመደባቸውም ታውቋል፡፡
ዋልያዎቹ ያለ የወዳጅነት ጨዋታ እየተዘጋጁ ናቸው፤ ምን ብለዋል?
ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በመጨረሻ ምርጫቸው የሚይዟቸውን 23 ተጨዋቾችን እስከትናት በስቲያ አላሳወቁም፡፡ እስከ ነገ ድረስ ከተለያዩ የውጭ አገራት የሚቀላቀሉትን ጨምሮ 30 ተጨዋቾች ዝግጅታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ለናይጄርያ ጨዋታ የሚሰለፉ 23 ተጨዋቾች ስም ዝርዝርን ሰኞ መገለፁ ይጠበቃል፡፡ በጊዜያዊነት የተመረጡት 28 ተጫዋቾች 10 ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ 4 ከደደቢት ሲሆኑ፣ ሦስት ሦስት ያስመረጡት ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናና የጎንደሩ ዳሽን ቢራ ናቸው፡፡ አርባ ምንጭ ሁለት ሲያስመርጥ፣ ሲዳማ ቡናና መከላከያ አንድ አንድ አስመርጠዋል፡፡ ሳምሶን አሰፋ፣ ደጉ ደበበ፣ ቢያድግልኝ ኤሊያስ፣ ሳላዲን በርጌቾ፣ አበባው ቡጣቆ፣ ምንያህል ተሾመ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ አዳነ ግርማ እና ዑመድ ኡክሪ ክቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ ሲሳይ ባንጫ፣ ብርሃኑ ቦጋለ፣ ሥዩም ተስፋዬና ዳዊት ፈቃዱ ከደደቢት፤ ጀማል ጣሰው፣ ቶክ ጀምስና ፋሲካ አስፋው ከኢትዮጵያ ቡና፤ ደረጀ ዓለሙ፣ ዓይናለም ኃይሉና አሥራት መገርሳ ከዳሸን ቢራ፤ ሙሉዓለም መስፍንና ገብረ ሚካኤል ያዕቆብ ከአርባምንጭ፤መድኃኔ ታደሰ ከመከላከያ፤ ሞገስ ታደሰ ከሲዳማ ቡና ከአገር ውስጥ የተመለመሉት ናቸው፡፡ ፤ ሳላዲን ሰይድ ከግብፁ ዋዲ ደጋላ፤ ጌታነህ ከበደ ከደቡብ አፍሪካ ቢድቪስት ዊትስ ፤ ሺመልስ በቀለ ከሊቢያው አልኢትሃድ እንዲሁም ፤ አዲስ ሕንፃ ከሱዳኑ አልሂላል እስከ ሰኞ ከቡድኑ ጋር እንደሚቀላቀሉ ነው፡፡

 አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድናቸው ወደ የዓለም ዋንጫ ጥሎ ለማለፍ በሜዳው ለሚጀምረው የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሲዘጋጁ ቢቆዩም በዚሁ ጊዜ የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ አቋማቸውን አለመፈተሻቸው መጠነኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ናይጄሪያን ከመግጠሙ በፊት ከጋና ወይም ከካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ታስቦ ነበር፡፡ ሁለቱም የምእራብ አፍሪካዎቹ አገራት ፕሮፌሽናል ተጨዋቾቻውን ማሳተፉ ስለከበደ ቢቀር ያሏቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ፌዴሬሽኑና ዋናው አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ለዓለም ዋንጫው ጥሎ ማለፍ ከደረሱት ቡድኖች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንዲደረግ ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ነበር፡፡ በዚህም ከምስራቅ አፍሪካ ቡድኖች ጋር በወዳጅነት ጨዋታዎች ያለው እድልን ለመጠቀም አልተቻለም፡፡ ግብፅ ወጭ ችላ በካይሮ ለመጫወት ያቀረበችው ጥያቄም ተቀባይነት አልነበረውም፡፡

ከጋና እና ካሜሮን ውጭ ለሌሎች ስድስት አገራት ደብዳቤ ተፅፎም ምላሽ አልተገኘም፡፡ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባይሳካለትም ናይጄርያም በአውሮፓ የሚገኙ ተጨዋቾቿን ቶሎ ለማሰባሰብ ስላዳገተ ትተዋለች። በአንፃሩ ግብፅ ከሴራሊዮንና ከኡጋንዳ ጋር፤ ጋና ከጃፓን ጋር እንዲሁም ቡርኪናፋሶ ደግሞ ከቦትስዋና ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎቻቸውን በማድረግ አቋማቸውን ፈትሸዋል፡፡ ዋሊያዎቹ ከንስሮቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ከቀረው የ1 ሳምንት ጊዜ አኳያ ዛሬ እና ነገ ካልሆነ በቀር በሚቀጥለው ሰሞን በየትኛውም ቀን የወዳጅነት ጨዋታ ማድረጋቸው አይጠቅምም፡፡ ተጨዋቾችን ለአላስፈላጊ ጉዳት እና የጨዋታ መደራረብ ስለሚፈጥር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ተጨዋቾች ከናይጄርያ ጋር ስለሚደረገው የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ በተለይ ለደቡብ አፍሪካው ሱፕር ስፖርት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ንስሮቹ በአዲስ አበባ ቀላል ተጋጣሚ እንደሚጠብቃቸው ማሰባቸው አግባብ እንዳልሆነ ያስጠነቀቀው በሊቢያው ክለብ አልኢትሃድ የሚጫወተው አማካዩ ሽመልስ በቀለ ነው፡፡ ‹‹በማይጠብቁት ሁኔታ እንፎካከራቸዋለን፡፡ ዋናው የጥንካሬያችን ምስጥር በቡድን ስራ የሚገለፅ ነው፡፡ እያንዳንዱ ተጨዋች ለዓለም ዋንጫ ለመድረስ ፤ ወደ ብራዚል የመጓዝ ህልም አለው፡፡ በናይጄርያው ጨዋታ መቶ በመቶ ብቃቴን ለማሳየት ዝግጁ ነኝ›› ብሏል። አጥቂው ሳላዲን ሰኢድም ናይጄርያውያን ከኢትዮጵያ ጋር ስለተደለደሉ ደስተኛ መሆናቸውን አጣጣጥሎታል።‹‹ ውጤቱ በሜዳ ላይ የሚወሰን ነው፡፡ ናይጄርያውያን ከእኛ ጋር መጫወትን በመናፋሻ ውስጥ እንደመንሸራሸር ከቆጠሩት ልክ አይደለም፡፡ ኢትዮጵይያ ለዓለም ዋንጫ መቼም ቢሆን በቅርብ ርቀት አልነበረችም፡፡ በጥሎ ማለፉ እስከመጨረሻው ደቂቃዎች በመፋለም እንጫወታለን› በማለት ተናግሯል፡፡

ሳላዲን ከሁለት ዓመት በፊት ጋር በአዲስ አበባ በተደረገ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ በናይጄርያ ላይ ሁለት ጎሎች ማግባቱ የሚታወስ ነው፡፡ ይህም በናይጄርያ መገናኛ ብዙሃናት በከፍተኛ ደረጃ እንዲፈራ አድርጎታል፡፡ ከሳምንት በኋላ በሚደረገው የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታም ጎል እንዳያገባብን ሳላዲን ሰኢድ ይያዝ ብለው ጥሪ ያቀረቡ አሉ ፡፡ ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተገናኙበት ወቅትም አስጨንቆ ነበር፡፡ ያኔ ደግሞ በግብ ጠባቂው ቪንሰንት ኢኒዬማ ላይ ከተሞከሩት ሶስት የግብ እድሎች ሁለቱን በአደገኛ ሁኔታ የሞከረው እሱ ነበር፡፡በደቡብ አፍሪካው ክለብ ዊትስ መጫወት ከጀመረ ሶስተኛ ወሩን የያዘው ጌታነህ ከበደም ከጉዳቱ በቂ ጊዜ ወስዶ በማገገም ከናይጄርያ ጋር በአዲስ አበባ የሚደረገውን ጨዋታ በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ለሱፕር ስፖርት ገልጿል፡፡ ከሴንተራል አፍሪካ ጋር በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የምድብ ማጣርያ የተደረገው ጨዋታ ስላመለጠው የቆጨው ጌታነህ ‹‹የአፍሪካን ሻምፒዮን እንደምንገጥም የታወቀ ነው፡፡

በቡድናችን ባለው የአንድነት መንፈስ ወደ ዓለምን ዋንጫ ለማለፍ የያዘነውን ህልም እናሳካለን› ብሏል፡፡ ሱፕር ስፖርት እንደዘገበው ጌታነህ ከበደ ከጉዳቱ በማገገም ለሳምንቱ ጨዋታ ይደርሳል። በደቡብ አፍሪካው ክለብ ቢድቪስት ዊትስ 6 ጨዋታ አድርጎ አራት ጎሎች ማግባቱ ግብ የማደን ብቃቱን ወቅታዊ እንደሚያሳይ ጠቅሶ በናይጄርያ ላይ ጫና በመፍጠር ለኢትዮጵያ ቡድን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብሎ ግምት ሰጥቶታል፡፡ ጌታነህ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተሰለፈባቸው 19 ጨዋታዎች 7 ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈ ነው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ በሰራናቸው ሁለት ስህተቶች ናይጄርያውያን ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች አግኝተው ማሸነፋቸውንና በቀይ ካርድ መሰናበቱን ያስታወሰው ግብ ጠባቂው ሲሳይ ባንጫ ነው፡፡
‹‹ስህተቶችን አንደግምም ናይጄርያን ለመበቀል በሜዳችን ከምናገኘው አጋጣሚ የተሻለ ሁኔታ የለም፡፡ በደጋፊያችን ፊት በአፈራችን ላይ ነው የምንጫወተው፡፡በደንብ እናሸንፋቸዋለን።›› ብሎም ለሱፕርስፖርት ተናግሯል፡፡ ዚስዴይ የተባለ የናይጄርያ ጋዜጣ የዘገበው ምን ያህል ተሾመ ለአዲስ ጉዳይ መፅሄት የሰጠውን አስተያየት ጠቅሶ ነው ፡፡ ተጨዋቹ ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ለማግኘት ናይጄርያ እንቅፋት አይሆንብንም እኛ የምናስበው ከናይጄርያም በላይ ነው፡፡ ዓለም ዋንጫ ገብተን ከስፔንና ከአርጀንቲና ጋር ባንድ ሜዳ መሰለፍን ተስፋ እናደርጋለን ማለቱን በማውሳት፡፡
ዋልያዎቹን ጥሎ ለማለፍ የጓጉት ንስሮቹና አጨናናቂ አጀንዳዎቻቸው
የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ከኢትዮጵያ ቡድን ጋር መደልደሉን ካረጋገጠ ወዲህ አጠቃላይ ዝግጅቱ በአጨናናቂ አጀንዳዎች ተወጥሮ ሰንብቷል፡፡ የመጀመርያው በየጨዋታው በሚከፈለው የሽልማት ገንዘብ የተፈጠረው አተካራ ነበር፡፡ ለነገሩ ከወሳኝ ፍልሚያዎች በፊት ቡድን ለማነሳሳት ይጠቅማል ተብሎ ጥሪ በማሰማት መስራት የተለመደ አሰራር ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ካለፉ ለእያንዳንዳቸው የመኪና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ በአንዳንድ አገራት እንደውም ለብሄራዊ ቡድኖቻቸው ተጨዋቾች በይፋ በሚገለፅ ሁኔታ በየጨዋታው በሚያስመዘግቡት ድል መሰረት የቦነስ ክፍያ የመስጠት አሰራር አላቸው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች እና በፌደሬሽኑ መካከል በየጨዋታው በሚገኝ የቦነስ ክፍያ መጠን የተፈጠረው አተካራ የሚነሳ ነው፡፡ ባለፈው ወር የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባለበት የገንዘብ ችግር ሳቢያ የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች በየጨዋታው በነፍስ ወከፍ የሚያገኙትን የቦነስ ክፍያ በ50 በመቶ ለመቀነስ ወስኖ ነበር፡፡ በየጨዋታው በነፍስ ወከፍ 5ሺ ዶላር ነው፡፡ ውሳኔው ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከኢትዮጵያ ጋር በሚደርገው ግጥሚያ ላይ ተፅእኖ እንዳይፈጥር በሚል ስጋት ለመቀየር ታስቦ አስቀድሞ እንደነበረው በነፍስ ወከፍ 10ሺ ዶላር ሊደረግ ይችላል እየተባለም ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የቦነስ ክፍያውን ለመቀነስ የታሰበው ስፖንሰሮች ቃል የገቡትን ገንዘብ በቶሎ ባለመስጠታቸው እንደሆነ ገልፆ ለኢትዮጵያው ጨዋታ የተለየ የቦነስ ሽልማት አልተዘጋጀም ብሎ አተካራውን ዘግቶታል፡፡
ንስሮቹን ወጥሮ የያዘው ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ በአዲስ አበባ ከፍተኛ አልቲትዩድ ሳቢያ በቡድኑ ላይ ሊፈጠር የሚችለው ጫና ነው፡፡ የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ብሄራዊ ቡድኑ ምንም አይነት የወዳጅነት ጨዋታ ሳይኖረው ቢያንስ በአቡጃ ተሰባስቦ ለአራት ቀናት ዝግጅት አድርጎ ለኢትዮጵያ ጨዋታ በዋዜማው ለመድረስ እቅድ እንዳለው አስታውቆ ነበር፡፡ በመጨረሻም በጨዋታው ዋዜማ ከመግባት ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ለመገኘት ተወስኗል፡፡ ኢትዮጵያውያን አየራችን ለናይጄርያ ይከብዳል ብለው መዘናጋታቸው ለውጤት ይጠቅመናል ያሉም አሉ፡፡ ከፍተኛ አልቲትዩድ ባላቸው አገራት ስንጫወት የመጀመርያ አይደለም ያሉት የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ አማካሪ ናቸው፡፡ አየሩን ለመላመድ ቢያንስ 10 ቀናት በኢትዮጵያ ለመቆየት ካልሆነልን በጨዋታው የዋዜማ ቀናት አዲስ አበባ በመግባት መጋጠማችን ተፅእኖ አይኖረውም ብለዋል፡፡ አንዳንድ የናይጄርያ መገናኛ ብዙሃናት ከሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ የሚደረገውን ጨዋታ ከሜዳ ውጭ በአስተማማኝ ሁኔታ አሸንፎ መመለስ በመልሱ በሜዳ ጥሎ ለማለፍ እንደሚያበቃ እየመከሩ ናቸው፡፡
የናይጄርያ ቡድን በኢትዮጵያ አቻው በመጀመርያ ጨዋታ የሚሸነፍ ከሆነ በመልሱ ከባድ ፈተና ውስጥ መግባቱ አይቀርም በማለትም ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በአሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ ለናይጄርያ ቡድን የተመረጡት 23 ተጨዋቾች የታወቁት ከሳምንት በፊት ነው፡፡ 18 ያህሉ በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ናይጄርያውያኑ ባለፈው አንድ ወር በየክለቦቻቸው ወሳኝ ሚና በመጫወት እና ጎሎችን ማግባታቸው ለኢትዮጵያ ጨዋታ እንደሚጠቅም ወቅታዊ ብቃት ተቆጥሯል። አምበልነቱ በግብ ጠባቂው ቪንሰንት ኢንዬማና ጆሴፍ ዮቦ መካከል እየዋለለ ነው፡፡

ይህ ፉክክርም ሌላው ንስሮችን የወጠረ ጉዳይ ነው፡፡ ጆሴፍ ዮቦ ቡድኑን በአምበልነት እንዲመራ እና ባለው ልምድ የተከላካይ መስመሩን እንዲያጠናክር በርካታ ግፊት እየተደረገ ነው፡፡ የእረፍት ግዜውን ከቤተሰቡ ጋር ለማሳለፍ ወደ አሜሪካ ተጉዞ የነበረው ስቴፈን ኬሺ በአቡጃ ከናይጄርያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ባለስልጣናት ጋር ስብስባ ነበረው ፡፡ በአቡጃ ቡድኑ በአገር ውስጥ በሚገኙ ተጨዋቾች ነገ ዝግጅቱን ሲጀምር በውጭ የሚገኙ ፕሮፌሽናሎች እስከሰኞ ይቀላቀላሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ስቴፈን ኬሺ የተመረጡ 23 ተጨዋቾች እስከ ፊታችን ሰኞ ሙሉ ለሙሉ ወደ ካምፕ ተጠቃለው እንዲገቡ ቀነ ገደብ ሰጥቶ ለ4 ቀናት ጠንከር ያለ ዝግጅት ለማድረግ መወሰኑ ታውቋል፡፡
ባለፉት ሶስት ሳምንታት በናይጄሪያ በርካታ መገናኛ ብዙሃናት ለኢትዮጵያ ጨዋታ ሰፊ ትኩረት እንደሰጡት ናቸው፡፡ ዘ ጋርድያን የተባለ አንድ የናይጄርያ ጋዜጣ የኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫው ጥሎ ማለፍ እቅድን ደርሼበታለሁ ብሎ ባቀረበው ሰፊ ሃተታ ዋልያዎቹ በሜዳቸው የሚያደርጉትን ጨዋታ በማንኛውም ሁኔታ ድል አድርገው በመልሱ ጨዋታ ከሜዳቸው ውጭ አቻ በመውጣት የደርሶ መልስ ትንቅንቁን በስኬት ለመጨረስ ያስባሉ ብሏል፡፡ አሁን የማላዊ ሰልጣኝ የሆኑት እና በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ያሰለጠኑት ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌት የናይጄርያ ተከላካዮች ከኢትዮጵያ አጥቂዎች ከባድ ፈተና እንደሚገጥማቸው አስጠንቅቀዋል።

የናይጄርያ ቡድን በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ብዙ ይቸገራል ያሉት ሴንትፌት ኢትዮጵያውያን ይህን ተገንዝበው ግብ ሊያስቆጥሩ ገልፀው እንደ ሳላዲን አይነት አጥቂዎች በዚህ አጨዋወት በቀላሉ ግብ ማስቆጠር እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች በሜዳቸው የሚያሳዩት ትእይንት ለንስሮቹ ያን ያህል አያስጨንቅም ያሉት የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ፀሃፊ ናቸው፡፡ በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ የነበረው ድጋፍ አሰጣጣቸውን እንደሚያስታውሱ አብራርተው በደጋፊ ብቻ ጨዋታን ማሸነፍ አይቻልም ብለዋል። ከኪክኦፍናይጄርያ መፅሄት ጋር ቪክተር ሞሰስ ባደረገው ቃለምልልስ የኢትዮጵያ ቡድን ለማሸነፍ የሚያስቸግር እና የሚከበር ነው ሲል ተናግሮ ‹‹በአፍሪካ ዋንጫ ያደረግነው ጨዋታን አስታውሳለሁ፡፡
ከባድ ፈተና ሰጥተውናል፡፡ እድለኞች ሆነን ባለቀ ሰዓት እኔ ላይ በፈፀሟቸው ሁለት ፋውሎች የተገኙት ኢሊጎሬዎችን አስቆጥሬ ነው አሸንፈን የወጣነው፡፡ በደንብ የተደራጀ፤ የአካል ብቃታቸው የጠነከረ፤ በማጥቃት አጨዋወታቸው አደገኛ እና ፈጣኖች ናቸው›› በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
ለቱርኩ ክለብ ፌነርባቼ የሚጫወተው ግዙፉ አጥቂ ኤምኒኬ ለኤምቲኤን ፉትቦል ድረገፅ በሰጠው ልዩ ቃለምልልስ የናይጄርያ ቡድን ባለበት የስኬት ደረጃ ምንም መጠራጠር እንደሌለበት ተናግሮ ብራዚል እንደሚጓዙ ሙሉ እምነት እንዳለው አስገንዝቧል፡፡ ዴቪድ ማርክ የተባሉ ሴናተር መላው ናይጄርያዊ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ለማሸነፍ እንዲያበረታታ በካቶሊክ አማኞች ለ9 ቀናት የሚዘልቅ የፀሎት ስነስርዓት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሴናተሩ ናይጄርያ በምንም አይነት ሁኔታ የብራዚል ዓከለም ዋንጫ ሊያመልጣት አይገባም ብለዋል፡፡ የቀድሞው የናይጄርያ አሰልጣኝ ሳምሶን ሲያ ሲያ ‹ከኢትዮጵያ ጋር በፊት ተጫውተናል፡፡ በተለይ በሜዳቸው አዲስ አበባ በጣም አስቸግረውናል፡፡ ቀላል ቡድን ብሎ ኢትዮጵያን መናቅ ለብስጭት ይዳርጋል፡፡ ከሜዳ ውጭ የሚደረገው ጨዋታ በጣም ወሳኝ ቢሆንም በሜዳም ለማሸነፍ በትኩረት መዘጋጀት ያስፈልጋል።› በማለት ምክሩን ለንስሮቹ አድርሷል፡፡
ከዓለም ዋንጫ ማግስት በኬንያ ሴካፋና በደቡብ አፍሪካ ቻን
ዋልያዎቹ በሚቀጥሉት ሳምንታት በዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ከናይጄርያ ከሚያደርጉት የደርሶ መልስ ትንቅንቅ በኋላ በሌሎች ሁለት ዞናዊ እና አህጉራዊ ውድድሮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ ሰሞኑን በመካከለኛው እና ምስራቅ አፍሪካ የእግር ኳስ ምክርቤት ወይም ሴካፋ የሚዘጋጀው የ2013 ሴካፋ ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕ በህዳር ወር አጋማሽ በተያዘው ፕሮግራም እንደሚካሄድ ዋና ፀሃፊው ኒኮላስ ሙንሶኜ አሳውቀዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳ ሃያቱ የውድድሩ የክብር እንግዳ እንደሚሆኑ የኬንያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ገልጿል፡፡ ካፍ ለውድድሩ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል የተባለ ሲሆን ከኦክቶበር 27 እስከ ኖቬምበር 12 የሚደረገውን ውድድር ኬንያ በአራት ስታድዬሞች ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቅቃለች፡፡

በኬንያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ አገራት ሻምፒዮና ላይ ለመካፈል 12 የዞኑ አባል አገራት ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ከማላዊ፤ ዛምቢያ፤ ዚምባቡዌ ወይም ኮትዲቯር መካከል ሁለት ተጋባዥ አገራት እንደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ለ3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ (ቻን) ውድድር ከሁለት ሳምንት በፊት የምድብ ድልድል ወጥቷል፡፡ በቻን ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ በምድብ 3 ከሊቢያ፤ ከጋና እና ከኮንጎ ብራዛቪል የተደለደለች ሲሆን በብሎምፎንቴይን በሚገኘው የፍሪ ስቴት ስታድዬም የምድብ ጨዋታዎቿን እንደምታደርግ ታውቋል። ጋና በቻን ውድድር ለሶስተኛ ጊዜ የምትሳተፍ ሲሆን በ2009 እኤአ የመጀመርያውን ዋንጫ ስትወስድ በ2011 እኤአ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች። ሊቢያ ለሁለተኛ ጊዜ በቻን ስትሳተፍ ኮንጎ እና ኢትዮጵያ የመጀመርያ ተሳተፏቸው ነው፡፡ በምድብ1 አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ፤ ማሊ፤ ናይጄርያ እና ሞዛምቢክ፤ በምድብ 2 ዚምባቡዌ፤ ኡጋንዳ፤ ቡርኪናፋሶ እና ሞሮኮ እንዲሁም በምድብ 4 ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ፤ ጋቦን፤ ቡርንዲና ሞውሪታንያ ተመድበዋል፡፡

 

               ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ለ2013 የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ በሁለቱም ፆታዎች የሚፎካከሩ እጩዎችን ስም ሲያስታውቅ ከእጩዎቹ መካከል ሶስት የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተካትተዋል፡፡ መሃመድ አማን ፤ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሠረት ደፋር ናቸው፡፡ አትሌት መሃመድ አማን በ800 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ከመሆኑም በላይ በርቀቱ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ለመሆን የበቃ እና በዓመቱ ካደረጋቸው 11 ውድድሮች አስሩን ያሸነፈ ነው፡፡ ዘንድሮ በ5ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው አትሌት መሰረት ደፋር በርቀቱ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ እንደሆነች ሲታወቅ በ3ሺ ሜትር እና በ10ሺ ሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ተሳክቶላታል፡፡ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በበኩሏ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ከመሆኗም በላይ በ10 ኪሎሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች፡፡

በኮከብ አትሌት ምርጫው በሁለቱም ፆታዎች ለመጨረሻ ምዕራፍ የሚደርሱትን ሶስት እጩ ተፎካካሪዎች ለመለየት በድረገፅ በሚሰጥ የድጋፍ ድምፅ ይሰራል፡፡ የዓለም የአትሌቲክስ ማህበረሰብን በማሳተፍ የሚከናወነው የምርጫ ሂደት ከተጀመረ ሶስት ቀን አልፎታል፡፡ ለሶስቱ የኢትዮጵያ ምርጥ አትሌቶች በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ድረገፅ (www.iaaf.org) አስፈላጊ የሆነውን ድምፅ በመስጠት ድጋፍ ሊሰጥ ይቻላል፡፡ እድሉ ለሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ በዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ታሪክ ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሸላሚ ሆነው ያውቃሉ፡፡ እነሱም በ1998 እኤአ የተሸለመው ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በ2004 እና በ2005 እኤአ አከታትሎ ያሸነፈው ቀነኒሳ በቀለ እና በ2007 እኤአ ላይ የተመረጠችው መሰረት ደፋር ናቸው፡፡

Saturday, 05 October 2013 11:09

የማራቶን ሪከርድ በኬንያዊ

ድጋሚ ተሰበረ፤ ከ2 ሰዓት በታች ይሮጣል ክርክሩ ቀጥሏል

      ከሳምንት በፊት በተደረገው የበርሊን ማራቶን በ31 ዓመቱ ኬንያዊ አትሌት ዊልሰን ኪፕሳንግ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ተሰበረ፡፡ አዲሱ የማራቶን ሪከርድ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ23 ሰኮንዶች ነው፡፡ ዊልሰን ኪፕሳንግ የዓለም ማራቶን ክብረወሰን ያሻሻለው ከሁለት ዓመት በፊት በሌላው ኬንያዊ አትሌት ፓትሪክ ተመዝግቦ ከነበረው 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ38 ሰኮንዶች የሆነ ጊዜ በ15 ሰኮንዶች ፈጥኖ በመግባቱ ነው፡፡ አዲሱን የዓለም ማራቶን ሪከርድ ካስመዘገበ በኋላ እንደ ኃይሌ ገብረስለሴ ክብረወሰኑን በድጋሚ ለማሻሻል የምችል አይመስለኝም ያለው ዊልሰን ኪፕሳንግ፤ ከእንግዲህ ትኩረቱ በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎችን ማግኘት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በበርሊን ማራቶን ለሁለት ጊዜያት የማራቶን ሪከርዶችን ያስመዘገበውና አራት ጊዜ ያሸነፈው ኃይሌ ገብረስላሴ ዘንድሮው ውድድሩን በማስጀመር ተሳታፊ ነበር፡፡ ዊልሰን ኪፕሳንግ አዲሱን የዓለም ማራቶን ሪከርድ ባስመዘገበ በማግስቱ በዓለም የአትሌቲክስ ማህበረሰብ እና መገናኛ ብዙሃናት ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ይገባል አይገባም የሚለው ክርክር በከፍተኛ ደረጃ አገርሽቷል፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት የዓለም ማራቶን ሪከርድ በበርሊን ሲሰበር የዘንድሮው ለስምንተኛ ጊዜ ነው በመሮጫው ጎዳና አመቺነታቸው የበርሊንና ለንደን ማራቶኖች ከ2 ሰዓት በታች የሚገባዎች መወዳዳርባቸው እንደሆነ ይገለፃል፡፡ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች እና እውቅ የማራቶን አትሌቶች በማራቶን ከ2 ሰዓት በታች የሚገባበትን ግዜ በአማካይ ከ20 እና ከ25 አመታት በኋላ የሚፈፀም ታሪክ መሆኑን እየገለፁ ቆይተዋል፡፡ ከሰሞኑ ግን በቅርብ አመታት የመሳካት እድል እንደሚኖረው ተዘግቧል፡፡ አዲሱን የዓለም ማራቶን ክብረወሰን የጨበጠው ኬንያዊ አትሌት ኪፕሳንግ የማራቶን ርቀትን ከ2 ሰዓት በታች መግባት እንደሚቻል ቢናገርም ለዚሁ ታሪካዊ ስኬት ራሱን በእጩነት ከማቅረብ ተቆጥቧል፡፡ ዘ ሳይንስ ኦፍ ስፖርት ከዓለም የማራቶን ፈጣን ሰዓቶች 80 በመቶው በሁለቱ የአፍሪካ አገራት ኬንያ እና ኢትዮጵያ በሚገኙ አትሌቶች የተመዘገበ መሆኑን በመጥቀስ ከ2 ሰዓት ሊገባ የሚችል አትሌትን የምናገኘው ከሁለቱ አገራት ነው በሚል ትንታኔ ሰርቷል፡፡

አሁን ካሉት የዓለማችን ታላላቅ የማራቶን ሯጮች ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ይገባሉ በሚል ከፍተኛ ግምት ባይሰጣቸውም የኬንያዎቹ ሞሰስ ሞሰፕ እና ኤልውድ ኪፕቾጌ፤ የኢትዮጵያዎቹ ቀነኒሳ በቀለ፣ አየለ አብሽሮ እና ፀጋዬ ከበደ እንዲሁም የእንግሊዙ ሞፋራህ በሚቀጥለው ዓመት አዲሱን የዊልሰን ኪፕሳንግ የማራቶን ክብረወሰን ለማሻሻል እንደሚችሉ እየተነገረላቸው ነው፡፡ ሞፋራህ በቀጣይ ዓመት ከትራክ ውድድር ወደ ማራቶን ሲሻገር ካሉት እቅዶች ዋንኛው ሪከርድ መስበር እንደሆነ ነው፡፡ የማራቶን ርቀትን ከ2 ሰዓት በታች ይገባል ቢልም እኔ አደርገዋለሁ ግን አላለም፡፡ ሞ ፋራህ ወደ ማራቶን ውድድር መግባቱን ለመደገፍ ታዋቂው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ በዓይነቱ የተለየ የመሮጫ ጫማ እየሰራለት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከሞ ፋራህ አሰልጣኝ አልበርቶ ሳልዛር ጋር በተደረገ ትብብር የሚዘጋጀው የናይኪ የመሮጫ ጫማ ከማራቶን ሰዓት እስከ 2 ደቂቃዎች ሊያተርፍ እንደሚችል ጥናት የተሰራበት ነው፡፡

አንዳንድ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ግን በትራክ የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች የዓለም እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ሞፋራህ በሁለቱ ርቀቶች ያሉት ፈጣን ሰዓቶች በኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከተያዙት ክብረወሰኖች በ15 ሰኮንዶች የዘገዩ መሆናቸውን በመግለፅ የእንግሊዛዊውን አትሌት ሪከርድ የመስበር እድል አጣጥለውታል፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ሞ ፋራህ ስኬታማ ከሆነበት የትራክ ውድድር ያለጥናት ወደ የማራቶን ውድድር ለመቀየር የገባውን ጥድፊያ ውጤታማ አያደርግህም ብሎታል፡፡ ከሞ ፋራህ ይልቅ የማራቶን ክብረወሰንን ለመስበር እድል ያለው ቀነኒሳ በቀለ እንደሆነም ዘገባዎች ጎን ለጎን ይመሰክራሉ፡፡ ከሳምንታት በፊት በቡፓ ግሬት ኖርዝ ራን አትሌቅ ቀነኒሳ በቀለ ሲያሸንፍ በመጨረሻዎቹ ሜትሮች ሞ ፋራህን ቀድሞ በመግባት ነበር፡፡ ይህ ውድድር ካለቀ በኋላ ሁለተኛ የወጣው ሞ ፋራህ “ለንደን እንገናኝ” ብሎ ቀነኒሳን ሲያናግረው “የሚጋብዙኝ ከሆነ ለመሳተፍ ዝግጁ ነኝ” ብሎ ምላሽ ሰጥቶታል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ2014 ወደ ማራቶን ሙሉ ለሙሉ ለመግባት እቅድ እንዳለው መናገሩ የሚታወስ ነው፡፡ በተለይ በ2016 በሪዮዲጄነሮ በሚካሄደው ኦሎምፒክ አገሩን በማራቶን ወክሎ በመወዳደር የወርቅ ሜዳልያ የማግኘት ሃሳብ እንዳለው ገልጿል፡፡ አሁን በዊልሰን ኪፕሳንግ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ23 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ከተያዘው ሪከርድ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት 204 ሰኮንዶች ይቀላሉ፡፡ ባለፉት አምስት አመታት ክብረወሰኖች በአማካይ 27 ሰኮንዶች ብቻ እየተሻሻሉ መቆየታቸው ታሪካዊውን ስኬት ለማግኘት እስከ 20 ዓመታት መጠበቁን ግድ ያደርገዋል፡፡ እንደስፖርት ሳይንቲስቶች ጥናት የሰው ልጅ የማራቶንን ርቀት ለመጨረስ በተፈጥሮ ብቃቱ ያለው የሰዓት ገደብ 1 ሰዓት ከ57 ደቂቃ ከ58 ሰኮንዶች ነው፡፡

                    በቅርቡ አንድ የመዲናችን የግል ኮሌጅ በሥራ አመራር የትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሲያስመርቅ፤ ግብረ ሰዶማዊነት በአገራችን እያስከተለ ስላለው አደጋ የሚያስቃኝ በጥናት የተደገፈ ጽሑፍ ቀርቦ ነበር፡፡ ፅሁፍ አቅራቢው፤ የግብረሰዶም አራማጆች ለኢትዮጵያ መንግስት “የመደራጀት መብታችን ይከበር” በሚል ያቀረቡትን ጥያቄና የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር የሰጡት ምላሽ በሚል ያቀረቡት ቀልድ ለአንባቢያን የሚያስተላልፈው ቁም ነገር አያጣምና ልጥቀሰው። ጠ/ሚኒስትሩ የመብት ጠያቂዎቹን ተወካዮች አስጠርተው እንዲህ አሏቸው፡-
“እንድትደራጁ ከመፍቀዳችን በፊት ጥያቄያችሁ ከሕግ፣ ከሞራል፣ ከባህል፣ ከሥነ ምግባር…አንፃር ተቀባይነት ይኖረው አይኖረው እንደሆነ ማጣራት አለብን፡፡ ይሄን ለማጣራት ደግሞ የእናንተም ትብብር ያስፈልገናል፡፡ የመጀመርያው ተግባራችሁ የሚሆነው የድጋፍ መጠየቂያ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ነው፡፡ የሰልፉ መነሻ መሐል መርካቶ ይሆናል፡፡ ድምፃችሁን እያሰማችሁ፣ መፈክሮቻችሁን በጽሑፍ ይዛችሁ በመጀመሪያ የምታልፉት በራጉኤል ቤተክርስቲያን በኩል ይሆናል፡፡ በመቀጠል አንዋር መስጊድን ታቋርጣላችሁ፡፡ ከዚያ ወደ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ትዘልቃላችሁ፡፡ በአፍንጮ በር በኩል በ6 ኪሎ ዩኒቨርስቲና የሰማዕታት ሐውልትን ካለፋችሁ በኋላ፣ በ4 ኪሎ ዩኒቨርስቲ በኩል የነፃነት ሐውልትን አቋርጣችሁ፣ በሁለቱ ቤተመንግስቶች መሐል በመጓዝ መስቀል አደባባይ መድረስ ከቻላችሁ፣ የመደራጀት ጥያቄያችሁ ምላሽ ያገኝ ይሆናል”
ቀልድ ነው ተብሎ የተነገረው የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ምላሽ በውስጡ ለውይይት የሚጋብዙ ሃሳቦችን ይዟል፡፡ በአገራችን ግብረሰዶም እንዳሁኑ የተስፋፋ አይሁን እንጂ ከግማሽ ክ/ዘመን በፊት ብቅ ብቅ ማለት መጀመሩን የሚጠቁሙ የአማርኛ ልቦለድ ሥራዎች አሉ፡፡
የአማርኛ አጭር ልቦለድ ጀማሪ ተብለው ከሚጠቀሱት ደራስያን አንዱ የሆነው ታደሰ ሊበን በ1949 ዓ.ም “መስከረም”፣ በ1952 ዓ.ም “ሌላው መንገድ” የተሰኙ ሁለት የአጫጭር ልቦለድ መድበሎች ያሳተመ ሲሆን ደራሲው በኢትዮጵያ ውስጥ የግብረ ሰዶማውያንን ሁኔታ የሚያመለክት ጭብጥ በማንሳት ፈር ቀዳጅ እንደሆነ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በ2000 ዓ.ም ያሳተመው ደራሲያንን የሚያስተዋውቅ አውደ እለት (አጀንዳ) ይጠቁማል፡፡
“ሌላው መንገድ” ስድስት አጫጭር ልቦለድ ታሪኮችን ያካተተ ሲሆን፤ በመጽሐፉ ከገጽ 55 እከ 74 የሚዘልቀው ታሪክ ዋና ገፀባሕሪ፣ ብርሃኑ የሚባል የ22 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ታሪኩን “እኔ” እያለ በአንደኛ መደብ የሚተርከው ገፀባህሪ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች ቼክ ክፍል ውስጥ ነው የሚሰራው፡፡
ከቁመቴ ማጠር በስተቀር ደም ግባቴ በጣም ቆንጆ ነበር፡፡ ይህንንም በየዕለቱ የተለያዩ ሰዎች በተለይ ሴቶች የሚያረጋግጡልኝ እውነት ነበር የሚለው ብርሃኑ፤ መልከመልካምነቱን ሲገልፅ፤ “ቀጥ ያለ አፍንጫ፣ ትክክል የሆኑና ንጣታቸው በረዶ የመሰሉ ጥርሶች፣ እጅግም ያልወፈሩ እጅግ በጣም ያልሳሱ መካከለኛ ከንፈሮች፣ ቅንድቦቼ የተኳሉና የተቀነደቡ የሚመስሉ፣ ፀጉሬ፣ ግንባሬ፣ ጉንጮቼ፣ ጆሮዎቼ፣ እምንም ዘንድ ያልተዛቡ፤ በጠቅላላው የሰራኝን እጅ ረቂቅነት አጉልተው የሚያወሱ ነበሩ። ለሴቶችም የማይችሉት ፈተና ነበርኩ…ሲያዩኝ መተርከክ፣ ማተኮር፣ መገላመጥ ግዴታቸው ነበር፡፡”
ጥሩ መልበስ ውበቴን ስለሚያጐላው አልባሌ ነገር መልበስ አዘወትር ነበር የሚለው ዋና ገፀ ባሕሪ፤ በ1942 ዓ.ም እለተ ሰኞ የገጠመውን ይተርካል። በቼክ ክፍል ለመገልገል የመጡ አንድ ደንበኛው ካስተናገዳቸው በኋላ፣ ለአንድ ጉዳይ እንደሚፈልጉት በመግለፅ እቤታቸው እንዲመጣ ይቀጥሩታል፡፡
ሰውየው በትልቅ ቪላ ቤት ውስጥ ነዋሪ ናቸው፡፡ የግቢ ጠባቂ ዘበኛ፣ የእልፍኝ አስከልካይ ወንድና ሴት አገልጋዮችም አሏቸው፡፡ መኖሪያ ቤታቸው ዘመናዊና በውድ ዕቃዎች የተሞላ ነው። ቀጠሮ የሰጡት ወጣት ሲመጣ፣ ውስኪ እየጋበዙ ያጫውቱት ጀመር። የእጅ ሰዓት ከኤደን (የመን) እንደሚያመጡለት ቃል ገቡለት፡፡ ሁለት ሙሉ ልብስ የሚያሰፋበትን ጨርቅ በአቅራቢያው ካለው ሱቅ እንዲወስድም ነገሩት፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ጉዱ የመጣው፡፡ “ሁሉ ሰው፣ መቼም ተፈጥሮ ሆኖ አንዳንድ አመል አለው” በማለት ፍላጐታቸውን በግልጽ ነገሩት፡፡
በቀረበለት ጥያቄ ግራ የተጋባው ብርሃኑ፤ “ምንም አልመለስኩለትም፤ ብቻ… አመዴ ቡን ብሎ ኩምሽሽ አልኩኝ” ይላል - የገጠመውን ሲተርክ። ከዚያም በብልሃት ከሰውየው ወጥመድ አምልጦ መውጣቱን ይተርካል፡፡
ነገሩ ከተከሰተ ከስድስት ወር በኋላም ሰውየው ተመሳሳይ ጥያቄ ለጓደኛው እንዳቀረቡለት ነግሮን ነው ታሪኩ የሚጠናቀቀው፡፡
“እሳት በሌለበት ጭስ አይኖርም” እንደሚባለው፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ ካየውና ከሰማው በመነሳት ከ50 ዓመት በፊት በአገራችን ግብረሰዶም ማቆጥቆጥ መጀመሩን በድርሰት ሥራው የጠቆመን ሌላኛው ደራሲ ኃይለሥላሴ ደስታ ነው፡፡ “የሚያቃጥል ፍቅር” በሚል ርዕስ በ1963 ዓ.ም ባሳተመው ለቦለድ መጽሐፉ፤ የዚህ ችግር ተጠቂ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ በጨረፍታ ያሳየናል፡፡
የመጽሐፉ ዋና ገፀ ባሕሪ ከትላልቅ ቤተሰቦች የተወለደች፣ ትምህርቷን ባሕር ማዶ ጭምር የተከታተለችና በህክምና ሙያ የሰራች ሲሆን የሕይወት ውጣ ውረድና መከራው በዝቶባት ከሐረር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በውቤ በረሃ የሴተኛ አዳሪነት ህይወቷ ከገጠሟት ያልተለመዱ ድርጊቶች አንዱን ትነግረናለች፡፡
የድርጊቱ ፈፃሚ በአየር መንገድ የሚሰራ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የግሉ ቪላ ቤትና የቤት አገልጋይ ሠራተኞች አሉት፡፡ ሴተኛ አዳሪዋን ከቡና ቤት አግኝቷት ነው ወደ ቤቱ የሚወስዳት፡፡ “ልብስሽን ሙሉ ለሙሉ አውልቀሽ ካልተኛሽ” በሚል ነው ያልተለመዱ ጥያቄዎችን ለዋና ገፀ ባሕሪዋ ማቅረብ የሚጀምረው፡፡
“ውስጥ ልብሴን እንኳን ልልበስ” ስትለው ሰውየው አይፈቀድላትም፡፡ “መጨረሻ ከሰው ቤት ነበርኩና ሳልወድ በግድ አወላልቄ ተኛሁ፡፡ ጥቂት ጊዜ እንደቆየን መብራቱ ጠፋና ‘ዙሪ’ አለኝ፡፡ በለሰለሰ አንደበት ‘ወዴት’ አልኩት፡፡ ‘ይህ ለሊት የእኔ ሥልጣን ነውና እንዳስፈለገኝ ላዝሽና ልጠቀምብሽ እችላለሁ’ አለ” እያለች የደረሰባትን ያልተለመደ እንግልትና በደል ትተርካለች፡፡
የአገር ውስጥ ገጠመኙ አይሁን እንጂ ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔርም የግብረ ሰዶማዊያን ባህሪና አቀራረብ ምን እንደሚመስል “ማስታወሻ” በሚል ርዕስ በደራሲ ዘነበ ወላ በተዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ አንድ ገጠመኙን በመጥቀስ ይነግረናል፡፡
ጉዳዩ በእንግሊዝ ለንደን የተከሰተ ነው። ስብሐት በወቅቱ ተማሪ ነው፡፡
ሃና የተባለች ፍቅረኛውን የሚያስተናግድበት እርካሽ የሆቴል መኝታ በመከራ ያገኛል፡፡ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ለስብሐት “እዚህ ሴት ይዞ መምጣት ክልክል ነው፡፡ ግን እኔ ሳላይህ ይዘህ መግባት ትችላለህ፡፡ እኔም እያየሁ አላይህም” እንዳለው ስብሃት ይነግረናል፡፡
“ሃና መጣችና ገና ከሩቅ እንዳየችው በእንግሊዝኛ ‘ያንን ሰው አልወደውም’ አለችኝ፤ ‘ምን ማለትሽ ነው’ አልኳት፡፡ ‘አንተን የሚያይበት አስተያየት ደስ አላለኝም’ አለችኝ፡፡ ‘ዝም ብለሽ ነው’ ብዬአት ባለውለታችን መሆኑን እያጫወትኳት ገባን፡፡ ተመላልሳ እዛ ሆቴል ትመጣለች፡፡ ሰውየውም አይቶ እንዳላየ ያሳልፈናል፡፡”
አንድ ቀን ሚስተር ዋትሰን ‘እንዲያው ፈገግታህ በጣም ደስ ይለኛል’ አለኝ፡፡
የሃና ዕይታ ተገለፀልኝ። የፍቅር ጨዋታን ከተቃራኒ ፆታ ጋር ሳይሆን ከተመሳሳዩ ጋር መደሰት የሚፈልግ ሰው ነው፡፡ በጨዋ ቋንቋ ልተባበረው እንደማልችል ነገርኩትና በሁኔታው እያዘንኩ ተለያየን፡፡”
በሦስቱ መፃሕፍት ውስጥ የቀረቡት መረጃዎች ሁለት ቁም ነገሮችን ያስጨብጡናል፡፡ አንደኛው አሁን ለአገራችን አደጋ ሆኖ የቀረበው ግብረ ሰዶማዊነት፤ መነሻው የባሕር ማዶ ልማድ መሆኑን ነው፡፡ ደራሲ ታደሰ ሊበን፤ በልቦለድ ስራው የዚህ ሰለባ መሆኑን የሚያሳየን ገፀባህሪ፤ ለንግድ ሥራ ወደ ውጭ አገራት የሚመላለስ ኢትዮጵያዊ ነጋዴ ነው፡፡
ደራሲ ኃይለሥላሴ ደስታም የቀረፀው ገፀባህሪ፤ ለውጭ የባህል ተጽእኖ በቀላሉ ሊጋለጥ የሚችል የአየር መንገድ ሠራተኛ ነው፡፡ ስብሐትና ፍቅረኛው ተግባሩን የተፀየፉት ሰውም እንዲሁ የውጭ አገር ዜጋ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን፤ ለትምህርት፣ ለሥራና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደተለያዩ የዓለም አገራት ሲመላለሱ ብዙ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ይዘዋቸው የሚመጡት አዳዲስ አፈንጋጭ ልማዶች ሕብረተሰቡ ሲፈቅድ ይስፋፋሉ። በተቃራኒው የማደግና የመስፋፋት ዕድል ያጡ ደግሞ አሉ፡፡
ከእነዚህም አንዱ ግብረ ሰዶም ነው፡፡ አሁን ግን ይሄ አፈንጋጭ ልማድ በአገራችን እየተስፋፋ መምጣቱና ለማህበረሰቡ አደጋ ሆኖ መጋረጡ እየተነገረ ነው፡፡
የቀድሞ ትውልድ የተቆጣጠረውን የማህበረሰብ ችግርና አደጋ፤ የአሁኑ ለምን መቆጣጠርና መከላከል አቃተው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ለውይይትም ይጋብዛል። ውይይቱ ከውጭ አገራት የሚገቡ ሌሎች መሰል አፈንጋጭ ልማዶችን ለመከላከል የሚያስችል ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት የሚሰጠን ይመስለኛል፡፡

Published in ጥበብ
Page 12 of 16