ብሩክታዊት ጐሳዬ ባለፈዉ ሳምንት በሀምሳ ዘጠኝ ግጥሞቿ-ፈክተዉም ቀዝዘዉም- ነፍስ የለገሱላትን መጽሐፍ አስመርቃለች። ያለ ተጨማሪ ክፍያ በለስላሳ ሙዚቃ የሰፈፉ ሰላሳ ግጥሞቿ በሚመስጥ አነባብና ድምፅ፥ ከምናባችን ለመፍታታት አቅም ነስንሳበት በሲዲ ለታዳሚ አበርክታለች። በድምጿ ቅላፄ ስንኝ ገፅ ላይ ሲወራጭ ያልፈረጠዉ የሆነ ሰመመን እየተረጨ እንመሰጣለን። “ማንነት” ግጥሟን“ሲነጋ ... ከቆመ ዕድሜዬ ላይ አንድ ቀን ሲሸረፍ” ብላ ነዉ የጀመረችዉ ስለ ስደትና ሀገር ሰቅቋት፤ የህይወትን ፈተና መግራት ሲመዘምዛት ከመስቀለኛ መንገድ አንዲት ነፍስ ስትሸበር ተቀንብቦበታል። ወደ ትዉልድ መንደር ሌጣዋን ለመመለስ ወይስ ከባዕድ ሀገር እንጀራዋን ለመጋገር ማድላት ከመሰለ አዙሪት መውደቅ ወላዋይ ያደርጋል። “እንደዚህ ነዉ ስደት፥ ከወገን መለየት/ ሃሣብ ብቻ ሳይሆን/ ማንነት ጧት ማታ የሚቀየርበት” እስከ መናዘዝ የሚያበቃ ያልሰከነ ግለ-ትዝብት ነዉ። ከዕድሜ አንድ ቀን የሚሸረፈዉ -የሚያጐነቁለዉ ሳይሆን- ለኑሮ የግለሰብ ህልም ሲገጣጠብ ነዉ። አመዛኝ ግጥሞቿ ለህላዌ ተምነሽንሸዉ መፍካትን ሳይሆን፥ ሥነልቦናዊና አካላዊ መፈነካከትን ቋጥረዋል። ሰአሊ ገጣሚ መስፍን ሃብተማሪያም በነፃ ግጥሙ የተቀኘዉን ያስታዉሰናል። “በጨለማዉ ጭንቅላቴ ዉስጥ/ የተንጠለጠሉት ሀሳቦች/ እንደ ቋንጣ ደርቀዋል/ .../ የሚስጥሬን አበባዎች ዝምታዬ ዉስጥ ቀበርኳቸዉ/ በስለዉም ሀዘን ሆኑ ”ለብሩክታዊት ግን በስለዉ እንጉርጉሮ ብቻ ሳይሆን ተስፋ፥ ስትበረታም መክሊቷ ናቸዉ፤ ፍቅር፥ ስደት፥ ሀገርና በሴት ጉዳይ መቆርቆር ወጥረዋታል። ግጥም ለኔ ትላለቻ ብሩክታዊት “... በስደት ... ለተጋፈጥኩት ሃይል ናፍቆት መግለጫ፥ በፅናት የሚያቆም አቅም ...” ነዉ። “የሚያቆስል ብቸኝነት ... የተለያዩ ቅፅበቶች የየራሳቸዉን ግጥሞች ጥለዉ አልፈዋል።” [ገፅ 5] ከምናቧ የፈሉ ብቻ ሳይሆን ከትዉልድ ስፍራዋ፥ ከባዕድ አገርም የኖረችዉን ያስተዋለችዉን፥ ከሌሎች ገጠመኝ ያጠነፈፈችዉን ይህን የህላዌ ቅፅበቶች ትዝታ ሳይገድፋቸዉ በግጥም -ቃል ሥጋ ሆነ በመሰለ አንድምታ- ረቀዉላታል።
የደበበ ሠይፉ “ለምን ሞተ ቢሉ” ጥያቄ ቢቆጠቁጠንም፥ ብሩክታዊት “እንዴት እንደኖረ” ይበልጥ ለብልቧት ነዉ ለምን ሞተ ቢሉን ሰክና ያውጠነጠነችበት። “ለምን ሞተ ቢሉ/ ንገሩ ለሁሉ/ ሳትደብቁ ከቶ፤/ `ከዘመን ተኳርፎ/ ከዘመን ተጣልቶ`።” በአፍላ ዕድሜው ነበር ደበበ ከዘመን መኳረፍ -ዉስብስብነቱ- ያስበረገገዉ። ብሩክታዊት የአንድ ግለሰብ መሞት ሣይሆን፥ ኑሮ ለሞት ሲዳርገው ነው የከነከናት።

ለፈረሰዉ አጥር፥ ለሚያፈሰዉ ጣራ
ሲሰራ ... ሲሰራ
ለተማሪ እህቱ ለታማሚ እናቱ
ሲሰራ ... ሲሰራ
እረፍት እንዳማረው
ሃገር እንዳማረው
ወዳጅ እንዳማረው
ነበር የኖረው
በሉና ንገሩው
(ያ ብቁ ወንድ ልጅ፥ ያ የህይወት ጀግና)
እንዴት እንደኖረ የጠየቁ ካሉ
እንዴት ሞተም ቢሉ
......................................
ናፍቆት ገዝግዞት
ሰዉ ማጣት ቦርቡሮት
....................................
ምናልባት ይሆናል
ነገን ሲገነባ ዛሬዉ ተንሸራቶ
የሰዉ ችግር ሲቀርፍ አዳማጭ አጥቶ።
[ገፅ 34-35]

ይህ “ያለአጥጋቢ ሰበብ”  የሚለዉ ግጥሟ በዘይቤ፥ በቁጭትና እሳቦት አንባቢን በሚፈትን ህሊናዊ ጥያቄ የረቀቀችበት ልዩ ግጥሟ ነዉ - አንድ ሁለት መወጠር የሚማጠኑ ስንኞች ያላደናገዙት። የተሰደደ ወጣት ከጐህ እስከ ዉድቅት ለቅርብ ዘመዶቹ ህይወት መቃናት፥ ድህነታቸዉን ለማሳፈር፥ ደስታቸዉን እያለመ ደከመኝ አለማለቱ ጐድቶታል። ግን አንጀት የሚለበልበዉ አካላዊ ልፋቱ ሣይሆን ከሀገሩ ርቆ “ናፍቆት ገዝግዞት/ ሰው ማጣት ቦርቡሮት”የዘመዶቹን ነገ ሲገነባ፣ የግሉ ዛሬነት አንሸራቶት ከመቃብር ወድቆ መቅረቱ ነዉ መራር -tragic- የሚያደርገው። አንድ ግለሰብ፥ ደበበ ለሌላ ዐውድ እንደተቀኘዉ “የክረምት ማገዶ” መሆን አለበት ወይ? እንዴት ብቻውን መስቀሉን ተሸክሞ ይንገዳገዳል? የጐረቤት ኮረዳ ፈገግታና ኩርፍያ  እንደናፈቀዉ፥ የአብሮ አደግ ጓደኞቹ ሣቅ እንዳባነነዉ፥ ከመንደሩ ተነጥሎ “ለፈረሰዉ አጥር፥ ለሚያፈሰዉ ጣራ” ላቡ እስኪነጠፍ ቢዳክር ምን ህላዌ ሆነ፤ ሰዋዊ ረብ አለዉ እራሱን እስከተቀማ ድረስ? እማዬ ምን ብበድል ነዉ ሁለት ጊዜ የሞትኩት፤ አንዴ በህይወት ሳለሁ፥ ዛሬ ነፍሴ ተስፈንጥራ ስትደፈጠጥ? ብሎ የጠየቀ እስኪመስለን ሰቅዞ የሚንጥ ግጥም ብሩክታዊት ተቀኝታለች። በዛወርቅ ያንጐራጐረችዉ “አገሬ እሄዳለሁ ይሄ አገሬ አይደለም/ ሚስጥር የሚያወያዩት አንድ ዘመድ የለም” የሚለዉ ትካዜ የማይመጥነዉ የተጠላለፍ ግጥም ነዉ።
    የበኩር መድበሏ በመሆኑ ብዙ ግጥሞቿ “ያለ አጥጋቢ ሰበብ ” ያመቀውን ቅኔያዊ ጥበብ መመጠን ተስኗቸዋል። ለመጥቀስ ያክል “ተመስገን” ፥ “ኩነኔ” ፥ “እጠብቃለሁ” ፥ “ሲገባኝ ” ... የመሳሰሉት በኑሮ እንቅስቃሴ የሆነ ስንጥቅ ያበጀ ትዝብት አልያም ገጠመኝ ሳያንሰዉ በቋንቋ አለመርቀቅ፥ የተለመደዉን ሁነት መፋቅ መኩላት ያቃተዉ፥ በፈዘዘ አማርኛ ስንኞች በመተንፈሳቸዉ ነው የተስለመለሙት። የዮሐንስ አድማሱ፥ የደበበ ሠይፉ፥ የነበይ መኮንን ከሁሉም በላቀ የፀጋዬ ገ/መድኅንን ግጥሞች አዝለው ወጣት ገጣሚያን -በተለይም ሴት ገጣሚያት- ሱባዔ ቢገቡ እንደ ሰለሞን ደሬሳ (በትኩስ ዕድሜዉ የአማርኛን ሥነግጥም ያማሰለና የለወጠ) ጥበባዊ ወኔ ባይጋባባቸውም ቢያንስ በአማርኛ ብቃታቸው አይታሙም፤ ከተራነት፥ በቋንቋም በእሳቦትም የመላቀቅ እልህ ሊያሯሩጣቸዉ ይገባል። ብሩክታዊት ጥቂት እንስት ደራሲያን የሚያደናቅፍ ራሮትነት -sentimentality- እምብዛም ሳይጐትታት ለመቀኘት መነሳቷ በራሱ ጥንካሬ ነዉ። መች ይሆን ከሴት ገጣሚያት አንድ ሁለቷ እንደ በዕዉቀቱ ሥዩም፥ በድሉ ዋቅጅራ፥ ኤፍሬም ሥዩም ... ገዝፈዉ ምናባችንን ጥሞናችንን ጐዝጉዘን የምንደመምባቸዉ? ያልተነካ እንጂ የተነካ ግልግል ስለማያውቅ ይህ የሚኮሰኩስ ጥያቄ ሊያወያይ ይገባል።
    በዕውቀቱ ሥዩም በአፍላ ዕድሜዉ ሴት ጓደኛን የኰነነበትን ግጥም አንብባ፣ ብሩክታዊት የተቀኘችበት መልስ ይመስጣል። ከ feminist -ለሴት ፆታ ተሟጋች- ባሻገር ለመርቀቅ ከአበቃት፥ ምነዉ የሌሎችንም አንብባ መልስ በፃፈች ያሰኛል። በአንድ ወቅት አንጋፋዉ ደራሲ አበራ ለማ፤ በሆነ ስዕል ለቀናት ተመስጦ እንደተቀኘዉ ብርቅ ግጥም ልቦናችንን ልንደቅንላት እንችል ነበር። “ያ መረቡ ልቤ ረገበ እምቢ አለ/ አንድ ራሱን ማስገር አቃተዉ ዋለለ”እንደ ተቀኘዉ አበራ፣ ብሩክታዊትም የሌላዉን እና ሌላዉን መመዘን ቢባባስባት ልዩ ግጥሞች በአነበብልናት። ለመሆኑ የብሩክታዊትን መልስ የለኮሰዉ የበዕዉቀቱ ግጥም ምን ነበር? ርዕሱ“አዳም እና ሚስቱ” ነዉ። “አዳም የትላንቱ/ የጥንት የጠዋቱ/ ሳይለፋ ሳይታክት ተኝቶ ባደረ/ ዉኃ አጣጭ አቻዉን ተጎኑ ተቸረ፤/ ይብላኝ ላ`ሁኑ አዳም ለታካች ምስኪኑ/ ምነዉ በተኛና በሸሸሁ ተጎኑ/ ለምትል ሔዋን።”  ንፅፅሩ የተላመድነውን ዕውነታ በለጋ እይታ እንድናጤነው ይቀሰቅሳል። ብሩክታዊት ለዚህ ጥባባዊ አንድምታ “ዕፀ-ሕይወት”ን ገጠመች።

ሄዋን ብትታደል ፈጣሪ ቢመርጣት
እስከመሞት ድረስ በ`ምነት የሚታዘዝ
ምርጥ አዳም ተሰጣት።
ይብላኝ ላ`ሁን ሄዋን
በበርጋጊ አዳሞች ተከባ ላለችዉ
እንኳን ዕፀ-በለስ
ዕፀ-ህይወት ብትሰጥ እምነቷን ላጣችዉ።

በርጋጊ አዳሞች “ሴት የላከዉ ...” ይባል እንጂ እንደ ሀረግ መሬት ለመሬት የሚሳበውን ሲያወላዉል “አለማወቅ” ትለዋለች በሌላ ግጥሟ። “አንድ ቀን ስጪኝ ይለኛል/ ይሄ ሞኝ ይሄ ያልገባዉ/ ምነዉ እርሱ ከቻለ/ ዘመኔን ሁሉ ቢወስደዉ።” ተባዕት መንፈዙ ይከነክናታል። ለዚህም ነዉ ወሲባዊ አንድምታ ሳይገድባት ሀሜትን በመስጋት ሴት ስዉር -invisible- ለመሆን እስከመመኘት የሚያበቃት፤ ገፅ 12 “ህልም ምኞት 1 ” ማጣጣም ይቻላል። ብሩክታዊት፥አንዲት እንስት ማኅበረሰቡ ያለበሳትን እድፍ ከአካሏና ህሊናዋ ለመግፈፍ ስትታክትና ስታውጠነጥን በግጥሞቿ ብትቀርፅም ሴትንም ጭምር ታዝባለች። “ሃሳቤን ቀይሬአለሁ” ፥ “እስከ መቼ” ፥ “ሁሉ አማረሽ”  የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።
    ገጣሚዋ ለመድበሏ የመረጠችዉ ስያሜ “ጾመኛ ፍቅር” ነዉ፤ የአንድ እምቅ ውብ ግጥም ርዕስ ነዉ። ስለ ፍቅር፥ የወንድና ሴት መፈቃቀድና መገፈታተር እንደ ጭብጥ የሀገር ጉዳይና የማንነት ጥያቄን እየታከከ ሌጣዉንም ተቀኝበታለች።
እህል ውሃ ተውኩኝ
ሱባዔ ገባሁኝ
ምኞቴን ለመናቅ ካልጋዬ ላይ ወረድኩ
ስጋዬን ልበድል ከፍሰሃ ታቀብኩ።
ስንቱን ንቄ ዉዬ
ስንቱን ችዬ ጾሜ
ሲያስገድፈኝ ያድራል
አንተን እያመጣ መናፍቁ ሕልሜ ።
አንዲት ሴት ፍቅረኛዋ ስለተሰደደ ወይም ምርር ብሏት ተገልላ፥ ከፍትወት ታቅባ ስሜቷን እየበደለች፥ “ጾመኛ ፍቅር” እንደ መሸሸግያ እየሆናት ለመዝለቅ ብትተጋም ፍቅርም ወሲብም ወጥመድ ሳይሆኑ ጥልቅ ጣዕም ናቸዉና ፈተና ነዉ።
አዳም ረታ በ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ልቦለዱ “ሊጥ” በሚለዉ ድንቅ ትረካዉ የቀረፃት ሰናይት ተመሳሳይ ገጠመኝ አላት። የልጅነት ፍቅረኛዋ ለመሰደድ ሲወስን “ገልዬ ፈራሁ” ብትለዉም “በዕድሜ የነተበ ጃኬቱ ላይ ዕንባዉን እየጠረገ” የሰዉ እጅ ማየት አንገሽግሾት ከሀገር ይኮበልላል። ብቻዋን ትቀራለች።
 “በየሄደችበት ተመልካች ታማልል የነበረችዉ” ሌላ ወንድ እንዳይደርስባት ለሰባት አመታት ትታቀባለች። ሆኖም “ጭንቀቷ ከመፈራረስ ይልቅ በየቀኑ ይደድራል፤ እና ታድያ ይደክማታል። በቀስታ ዉስጧን የሚሰረስር፥ እስከ አጥንቷ ዕንብርት ቁርጥማት እየበላት የሚዘልቅ ነበር።” ስጋዊ ረሃብን በስራ ለማፈን መጣር ህመምም ነዉ።
ብሩክታዊት የተቀኘችላት የፍቅር ጾመኛ ኮረዳነቷ እንደ እሳት የሚያቃጥላት፥ ከተናገረችዉ የሸሸገችዉ ቢያመዝንም፥ “ሲያስገድፈኝ ያድራል/ አንተን እያመጣ መናፍቁ ሕልሜ” ፈተና ሆነባት። ይህ በዘይቤ የረቀቀ ግጥም ሴት ልጅ በሆነ ምክንያት -በማፍቀርም፥ ላለማፍቀርም- ስሜቷን ስትገድብ ለዚያ ወንድ መስገብገቧ እንደሆነ ህልሟን ጭምር ያዉከዋል። ፍቅር ገድፎ ለኅላዌ ጣዕም መቦረቅና ማሩን መጋገር ምን ሀይል ያሟሽሸዋል ? በሌላ ግጥሟ እንዳፈረጠችዉ ነዉ ሴት መፈለጓና መጥላቷ አያዎነቱ የሚደንቀን።
“እንዳትመጣ ብዬህ/ እንዳላይህ ብዬህ/ ካለህበት ላልኖር ምዬ ተገዝቼ/ እየጠበቅኩህ ነዉ ናፍቄ ጓጉቼ” ህይወት እንዲህ ናት፤ የማኅበረሰብና የግል ዕይታ ተፃራሪ ፍላጎት ይፋተጉበታል፤ ደግነቱ ባለቅኔ በስንኞቹ እየፈተለ ያስተዛዝበናል፤ ከመሆን አለመሆን ጥያቄ ዛሬም አርነት የወጡት ጥቂት ናቸዉና። ብሩክታዊት በሃሌታ መድበሏ ካወያየችን፥ ጠነን ባሉ ተናዳፊ ግጥሞቿ በለጣቂ ስብስብ መጽሐፏ ልናነብላት፥ ልንመሰጥባት ገርታናለች። ያዉ ገጣሚ -ብሩክታዊትም- በዕዉቀቱ ስዩም እንዳለዉ “... በጭብጨባ ብዛት የማይለመልም፥ በእርግማን ብዛት የማይከስም ... ለሰዉ ልጆች የሚገደዉ (የሚገዳት) ” ነዉ፤ ናትም።

Published in ጥበብ

   2015 እኤአ ከገባ በኋላ ባለፈው አንድ ወር የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተካሄዱ የማራቶን ውድድሮችን እያሸነፉ ናቸው፡፡ የትናንቱን የዱባይ ማራቶን ጨምሮ ከአራት በላይ ውድድሮችን የኢትዮጵያ አትሌቶች በፍፁም የበላይነት አሸንፈዋል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያኑ በሚቀጥሉት አራት ወራት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በሚደረጉ ትልልቅ ማራቶን ውድድሮችም በብዛት እና በከፍተኛ ደረጃ የተሳትፎ ግብዣ እያገኙ ናቸው፡፡
ዱባይ ማራቶን
ትናንት በተካሄደው የዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያዊ አትሌቶች ፍፁም የበላይነት አሳይተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶች ምድብ ከ1 እስከ 10 ደረጃ ሲያገኙ፤ በሴቶች ደግሞ ከ1 እስከ 10 ባለው ደረጃ ስምንት ገብተዋል፡፡ ከዓለም ማራቶን ውድድሮች ከፍተኛ ሽልማት በሚቀርብበት የዱባይ ማራቶን ከ1 እስከ  10 በሁለቱም ፆታዎች ለሚወጡ አትሌቶች ከተዘጋጀው 800ሺ ዶላር ኢትዮጵያውያኑ 678800 ዶላሩን አፍሰዋል፡፡ በወንዶች 399400 ዶላር እንዲሁም በሴቶች 279 400 ዶላር ማለት ነው፡፡ በሴቶች ምድብ አስደናቂ ድል ያስመዘገበችው ልጅ ከወለደች ከ18 ወራት በኋላ የመጀመርያ ማራቶኗን ያደረገችው አሰለፈች መርጊያ ናት፡፡ አሰለፈች መርጊያ  በዱባይ ማራቶን ስታሸንፍ ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን በውድድሩ ታሪክ ይህን ማሳካት ከቻሉት ኬንያዊው ዊልሰን ኪቤት እና ኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገብረስላሴ ጋር ክብረወሰን ተጋርታለች፡፡ አሰለፈች መርጊያ የዱባይ ማራቶንን ያሸነፈችው ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃዎች ከ02 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ነው፡፡ አሰለፈችን ተከትለው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ሁለት ኬንያውያን አትሌቶች ሲያስመዘግቡ ከአራተኛ እስከ አስርኛ ያለውን ደረጃ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አግኝተዋል፡፡ በወንዶች ምድብ ያሸነፈው  ደግሞ ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ብርሃኑ ሃይሌ ሲሆን ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃዎች ከ28 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ በመሸፈን ነው፡፡ እሱን በመከተል እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ኢትዮጵያውያን አከታትለው ወስደዋል፡፡
በማራቶን ለሶስተኛ ጊዜ ለመወዳደር ዱባይ ማራቶንን የተሳተፈው እና ከፍተኛ ውጤት እንደሚያመጣ ተጠብቆ የነበረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከ36 ኪሎሜትር በኋላ አቋርጦ ወጥቷል፡፡ ከዓመት በፊት የመጀመርያ የማራቶን ቅውድድሩን በፓሪስ ማራቶን አድርጎ የቦታውን ሪከርድ በማስመዝገብ ካሸነፈ ከ27 ሳምንታት በኋላ ቺካጐ ማራቶንን በመሮጥ አራተኛ ደረጃ አግኝቶ የነበረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፤ ከ15 ሳምንታት በኋላ የዱባይ ማራቶንን ቢሳተፍም ውድድሩን ለማቋረጥ ግድ ሆኖበታል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከ13 ሳምንታት በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ሊሰበርበት ይችላል በተበለው የ2015 ለንደን ማራቶን እንደሚሮጥ ይጠበቃል፡፡
በሙምባይ እና ሂውሰተን ማራቶኖች
በሌላ በኩል ባለፉት ሳምንታት ሁለት ማራቶኖች በተለያዩ ሁለት አህጉራት ተካሂደው ኢትዮጵያዊ ማራቶኒስቶች ድንቅ የበላይነት አሳይተዋል፡፡ በኤስያ አህጉር ህንድ ላይ ተደርጎ በነበረው የሙምባይ ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያውያኑ ተሳክቶላቸዋል፡፡
በወንዶች ምድብ የመጀመርያ የማራቶን ውድድሩን የሮጠው አትሌት ተስፋዬ አበራ ርቀቱን በ2 ሰዓት 09 ደቂቃ ከ46 ሰከንዶች በመሸፈን ሲያሸንፍ የቦታውን ክብረወሰን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት አድርጎ በ14 ሰከንዶች ዘግይቶ በመግባቱ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ እሱን በመከተል በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ደረጄ ደበሌ ነው፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የሙምባይ ማራቶንን በማሸነፍ ክብሯን ያስጠበቀችው ርቀረቱን በ2 ሰዓት ከ30 ደቂቃዎች የሸፈነችው ድንቅነሽ መካሻ ስትሆን ሌሎቹ ኢትዮጵያውያውያን ኩምሺ ሲቻላ እና ማርታ ዋግራ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡ የሙምባይ ማራቶን አሸናፊዎች ለእያንዳንዳቸው በሁለቱም ፆታዎች 41ሺ ዶላር ይበረከትላቸዋል፡፡ በተያያዘ በዚያው ሰሞን ለ43ኛ ጊዜ በአሜሪካ በተደረገው የሂውስተን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለሰባተኛ ተከታታይ አመት በውድድሩ ያለመሸነፍ ክብራቸውን አስጠብቀዋል፡፡ በሂውሰተን ማራቶን ላይ በወንዶች ምድብ ብርሃኑ ገደፋ በ2 ሰዓት ከ08 ደቂቃዎች ከ30 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ የግሉን ምርጥ ሰዓት አስመዝግቦ ሲያሸንፍ በሴቶች ደግሞ ያበሩኛል አራጌ ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ23 ደቂቃዎች ከ33 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ በመጨረስ ድል አድርጋለች፡፡
በለንደን ማራቶን
የ2015 ለንደን ማራቶን ከ13 ሳምንታት በኋላ ምርጥ አትሌቶች የሚካሄድ ነው ፡፡
 ከኃይሌ ገ/ስላሴ በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርዱን አፈራርቀው የሰሩበት ኬንያዊያኑ ዊልሰን ኪፕ ሳንግና ዴኒስ ኮሚቴ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ደግሞ ፀጋዬ መኮንን (2፡04፡32) አየለ አብሽሮ (2፡04፡27) ይጠቀሳሉ፡፡  በ2015 ለንደን ማራቶን ላይ ለወንዶች ምድብ የሚሳተፉት ምርጥ አትሌቶች ከ2፡05 በታች የሚገቡ 8 አትሌቶች፣ ለዓለመ የማራቶን ምርጥ ሰዓት ደረጃ ከ1-10 ካለው 5ቱ እንዲሁም 4ኛ ማራቶን ውድድሩን የሚያደርገውና የ10ሺህ የ5ሺሜ ሪኮርዶችን ከያዘ ከ10 ዓመት በላይ ያስቆጠረው ቀነኒሣ በቀለ ናቸው፡፡ በሴቶች ምድብ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩት ሁለት አትሌቶች ብቻ ሲሆኑ ፋይሴ ታደሰ እና ትግስት ቱፋ ናቸው፡፡
በፓሪስ ማራቶን
 ከ13 ሳምንታት በኋላ በሚደረገው የ2015 የፓሪስ ማራቶን ከ1 ዓመት በፊት በቀነኒሣ በቀለ የመጀመሪያ ማራቶን የተሻሻለውን የቦታውን ክብረወሰን ለመሰበር ከባድ ተወዳዳሪዎች ይገባሉ፡፡ በወንዶች የሚሳተፉት ኢትዮጵያውያን ደሬሳ ቺምሣ (2፡05፡42) ባዙ ወርቅ (2፡05፡25) ፣ ሰቦቃ ቶላ (2፡06፡17)፣ ራጂ አሰፋ (2፡06፡24) ናቸው፡፡ በሴቶች ደግሞ ሙሉ ሰቦቃ (2፡23፡13) እና አማን ጐበና (2፡23፡50) ናቸው፡፡
በቦስተን ማራቶን
ከዓለማችን የማራቶን ውድድሮች አንጋፋው በሆነው የቦስተን ማራቶን 9 የኢትዮጵያ አትሌቶች ተሳታፊ ናቸው፡፡ በወንዶች ምድብ ለሁለት ጊዜያት የቦስተን ማራቶንን ያሸነፈው ሌሊሳ ዴሲሳ፤ የማነ ፀጋዬ፤ ታደሰ ቶላ እና ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም ሲሳተፉ፤ 20154 ከገባ በኋላ በቻይና የተደረገውን የዣይናሜን ማራቶንን ያሸነፈችው ማሬ ዲባባ፤ አምና የቦስተን ማራቶን አሸናፊ የሆነችው ብዙነሽ ዳባ፤ አበሩ ከበደ፤ ማሚቱ ደስካ እና እጅጋየሁ ዲባባ ይወዳደራሉ፡፡




ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 1.3 ሚሊዮን ብር  ከህጻናትና፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን ጋር ለሚሰሩ  4 ሀገር በቀል ድርጅቶችን አበረከተ፡፡ ገንዘቡ ከወራት በፊት ከ40ሺ በላይ ስፖርተኞችን ባሳተፈው 14ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10ኪ.ሜ ሩጫ በተያያዘ በተደረገው የዕርዳታ ማሰባሰብ ስራ የተገኘ ነው ፡፡  ከዘንድሮ  4 ተጠቃሚዎች  ባለፈው ሐሙስ የገንዘብ ርክብክቡ የተፈፀመበት እና የመስክ ጉብኝት የተደረገበት በኦሮምያ ክልል ደብረሊባኖስ ገዳም አካባቢ የሚገኘው ሰዋሰው ገነት የልማትና የዕርዳታ ድርጅት የመጀመርያው ነው፡፡ ሌሎቹ ሶስት ድርጅቶች ደግሞ መሰረት የበጐ አድራጐት ድርጅት ፤ በጋምቤላ የሚገኘው ብራዘርስ ኤንድ ሲስተርስ ቺልድረን ኬር ሴንተር እንዲሁም የቤንሻንጉል ሴቶች ማህበር ናቸው፡፡የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ላቀረበው የድጋፍ ጥያቄ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ፈጥኖ መድረሱን በርክክቡ ወቅት የገለፁት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዘነቡ ፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየጊዜው ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ተወካይ ሚስተር ፖስቲ ያዮ በበኩላቸው ፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚያዘጋጀው ውድድር ጎን ለጎን ለእርዳታ በሚያሰባስበው ገንዘብ ብቻ እንዳልተወሰነ ጠቅሰው የሚሊኒዬም የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ ጠቃሚ መልክቶችን በየክልሉ እና በየውድድሮቹ በማስተላለፍ አጋዥ ተቋም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በእርዳታ ለአራቱ ድርጅቶች የተከፋፈለው ገንብ በአራት መንገዶች መሰባሰቡን  የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድር ዲያሬክተር አቶ ኤርምያስ አየለ ገልጿል፡፡ ዘንድሮ ከተሰበሰበው ገንዘብ ግማሹ የተገኘው  በኖርዌይ ሩጫ ከሚያዘጋጅ ክለርቪክሚለር ከሚባል ድርጅት በአጋርነት በመንቀሳቀስ ነው፡፡ ውድድሩ ሲደርስ ለትልልቅ ድርጅቶች ደብዳቤ በመፃፃፍ ልገሳዎች ተገኝተዋል፡፡ የታላቁ ሩጫ መወዳደርያ ቲሸርቶችን በልዩ ዋጋ ጭማሪ በመሸጥና ተወዳዳሪዎች በግላቸው እርዳታ በማሰባሰብ እንዲሮጡ በማበረታታት የተቀረው ገንዘብ ገብቷል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው በተያያዘ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ለአገር በቀል የዕርዳታ ድርጅቶች ገንዘብ በማሰባሰብ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴርና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ (UN Ethiopia) ጋር በመተባበር ይንቀሳቀሳል፡፡
 እስከ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብም ለ20 ድርጅቶች አከፋፍሏል፡፡ ተጠቃሚ ለመሆን ከቻሉት መካከል ሜሪ ጆይ፣ አበበች ጐበና የህጻናት ማሳደጊያ፣ ሜቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ይገኙበታል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድር ዲያሬክተር አቶ ኤርምያስ አየለ በሚቀጥሉት ዓመታት የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለማሳደግ መታቀዱን አስታውቋል፡፡ ተጠቃሚ የሚሆኑ ድርጅቶች ከወዲሁ በሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ቢሮ አማካኝነት ይመረጣሉም ብሏል፡፡በመላው ዓለም የሩጫ አዘጋጅ ድርጅቶች ለበጎ አድራጎት ስራ የሚውል ከፍተኛ ገንዘብ የሚሰበሰብባቸው መድረኮች መሆናቸውን የሚያመለክተው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ይህን መልካም ልምድ በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡
 የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች በአገራችን ከሩጫ ጎን ለጎን እርዳታ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች መደገፍ ይቻል ዘንድ በሩጫ ውድድር ላይ ለጤናና ለመደሰት ከመሮጥ ባሻገር ለአንድ በጎ ምክንያት በመሮጥአስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚቻል ይመክራሉ፡፡

በቅርቡ በ6 የክልል ከተሞች አገልግሎት ለመስጠት አቅዷል
   አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ በአራት የሀክምና ምርመራ ዘርፎች ማለትም በኬሚስትሪ፣ በሔማቶዘሎጂ፣ በኢንዶክሪኖሎጂና በሴሮሎጂ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሪዲቴሽን ጽ/ቤት የእውቅና ሰርተፍኬት አገኘ፡፡
ድርጅቱ ይህንኑ የእውቅና ሰርተፍኬት አቀባበል ሥነስርዓትን ከትናንት በስቲያ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ውስጥ ሲያካሂድ እንደተገለፀው እውቅናው አገር አቀፋዊና አህጉር አቀፋዊ የሆነ የላብራቶሪ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ጥርጊያ መንገድ ከፋች ነው ተብሏል፡፡
ላለፉት 42 ዓመታት እጅግ ዘመናዊ በሆኑ የላብራቶሪ መሣሪያዎችና በሰለጠኑ ባለሙያዎች ከ300 በላይ የሚሆኑ የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የሚኙት አብዛኛዎቹ የላብራቶሪ መመርመሪያ መሣሪያዎች ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ደረጃዎች የጠበቁ መሆናቸውን የገለፁት የድርጅቱ የፋይናንስና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ብቅአለ መስፍን በመሣሪያዎቹ ዋጋ ከፍተኛነትና በሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት በአገር ውስጥ ማድረግ የማይቻሉ አንዳንድ ምርመራዎችን ወደ እንግሊዝ፣ ጀርመንና ደቡብ አፍሪካ ናሙናዎችን በመላክ ውጤቱን በኢሜይል በመቀበል ለተመራማሪዎች የሚያስረክብ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ድርጅቱ አሁን የእውቅና ሰርተፍኬት ካገኘባቸው የህክምና ምርመራ ዘርፎች በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎችም በተለይም በማይክሮ ባዮሎጂ የእውቅና ሰርተፍኬት ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም በዚሁ ወቅት ገልፀዋል፡፡ የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ዘለዓለም ፍሰሃ ድርጅቱ ለረጅም ጊዜ ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው የህክምና ምርመራ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ገልፀው አሁን ያገኙት እውቅና በአራት ትላልቅ የምርመራ ዘርፎች ሆኖ በሥሩ በርካታ የምርመራ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችላቸው እንደሆነና ይህም ቀደም ሲል በአገር ውስጥ የማይሰሩ ምርመራዎችን ለማድረግ የሚያስችላቸውና እየተሰሩ ያሉትንም የላብራቶሪ አገልግሎች የጥራት ደረጃ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ ከፍተኛ አቅምና ብቁ መሣሪያዎች ያሉት ድርጅት ነው ያሉት ዳይሬክተሯ በአሁኑ ወቅት እየተጠቀመ ያለው የአቅሙን 30 በመቶ ብቻ መሆኑንና ይህንን ለማሳደግም ከፍተኛ ጥረት በመዳረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ በ6 የአገሪቱ የክልል ከተሞች ማለትም በድሬዳዋ፣ አዋሣ፣ ባህርዳር፣ ጐንደርና ትግራይ ላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ገልፀዋል፡፡ በ1965 ዓ.ም በአርመናዊው ተወላጅ በዶ/ር አርሾቬር ቴሪዚያን የተመሰረተውና በአገሪቱ የመጀመሪያው የግል የህክምና ላብራቶሪ እንደሆነ የሚነገርለት አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ 6 ቅርንጫፎቹ የህክምና ምርመራ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

Published in ዋናው ጤና

በ300 ሚ. ዶላር ኢትዮ አሜሪካን ዶክተርስ ስኩል ሊገነባ ነው

“ከአገሬ ወጥቼ ዘመኔን በስደት አሳልፋለሁ የሚል ምኞትና ህልም ፈፅሞ አልነበረኝም፡፡ የቀዶ ህክምና ትምህርቴን በ1976 ዓ.ም አጠናቅቄ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሙያዬ እየሰራሁ ባለበት ወቅት አገሬን ጥዬ ለስደት እንድዳረግ የሚያስገድድ አጋጣሚ ደረሰብኝ፡፡ በቤተሰቦቼና በጓደኞቼ ላይ የደረሰው አደጋ አስደንግጦኝ ስደትን መረጥኩ፡፡ መጀመሪያ የሄድኩት ወደ አውስትራሊያ ነበር፡፡ ከዚያ ወደ አሜሪካ ቴክሳስ፣ በመቀጠልም ወደ ኒውዮርክ አምርቼ ኒውዮርክ ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ የውስጥ ደዌ ህክምና አጠናሁ፡፡ በዚሁ ኮሌጅ ለአምስት አመታት በአስተማሪነት አገልግያለሁ፡፡ ላለፉት ሰላሳ አመታት በህክምና ማማከር አገልግሎት፣ በማገገሚያ ማዕከላትና በበጎ ፍቃደኝነት ደግሞ በአልበርት አንስታይን ኮሌጅ ኦፍ ሜዲስን ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡
“ወደ አገሬ ተመልሼ ለመግባትና በሙያዬ ወገኖቼን ለማገልገል እንድወስን ያደረገኝ ግን አሜሪካ አገር ከሚኖሩና እኔ ከምከታተላቸው ህመምተኞች የተሰጠኝ ምላሽ ነበር፡፡ በአሜሪካ አብዛኛዎቹ በእኛ ዘመን የተሰደዱ ሰዎች እድሜያቸው የገፋና ጡረታ የወጡ ናቸው፡፡ ለምን ወደ አገራችሁ አትገቡም? ስላቸው፣ ሐኪም ወደሌለበት ቦታ ሄደን ችግር ላይ እንወድቃለን ይሉኝ ነበር፡፡ እኔ ብሔድስ ስላቸው፣ ያኔማ እኛም እንገባለን… የሚል ምላሽ ይሰጡኛል፡፡ ይህ ነገር በውስጤ የሆነ ነገር እንዲጫርና ወደ አገሬ ለመግባት ልቤ እንዲነሳሳ ምክንያት ሆነኝ፡፡ እንደ እኔ ወደ አገራቸው ለመግባት ፍላጎቱ ካላቸው፣ ከህክምና ባለሙያ ጓደኞቼ ጋር በመሆን፣ ወደ አገራችን ገብተን በሙያችን ወገኖቻችንን ማገልገል እንዳለብን አሰብን፡፡ እናም ይህንን የጤና ማዕከል ልናቋቁም በቃን፡፡” ይህንን ያሉኝ ባለፈው ቅዳሜ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የዋሽንግተን ሜዲካል ሴንተር ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ፋሲል ተፈራ ናቸው፡፡ በአሜሪካ አገር ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ በህክምና ሙያ ሲያገለግሉ በቆዩ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሀኪሞችና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች  ጥምረት የተቋቋመው ዋሽንግተን ሜዲካል ሴንተር፣ 60 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን ዘመኑ ባፈራቸው ዘመናዊ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች የተደራጀ መሆኑን የህክምና ማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ ተናግረዋል፡፡ በውስጥ ደዌ ህክምና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ማዕከሉ፤ በዘመናዊ የኤክስሬይ፣ አልትራ ሳውንድ፣ ኢኬጂና ላብራቶሪ ክፍሎች የተደራጀ ሲሆን ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ለሆኑ ዲፕሎማቶችና የውጪ አገር ሰዎች የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ማዕከል መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
“ማዕከሉ ዋሽንግተን ሜዲካል ሴንተር የሚል ስያሜ እንዲሰጠው የወሰንበት ዋንኛ ምክንያታችን በዚያ የስደት ዘመን መጠጊያና መሸሸጊያ አጥተን በነበረበት ወቅት በሯን ከፍታ የተቀበለችን ከተማ ዋሽንግተን በመሆኗ ለእሷ መታሰቢያ እንዲሆን በማሰብ ነው” ያሉት የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ፋሲል ተፈራ፤ እንደ እኛ ሁሉ ወደ አገራቸው በመመለስ ወገኖቻቸውን ለማገልገል የሚፈልጉ በርካታ የጤና ባለሙያዎች እኛ የጀመርነውን ፈር በመከተል ወደ አገራቸው በቅርቡ እንደሚመለሱ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡ አሜሪካንን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎችን ያካተተውና ከ250 በላይ አባላት ያሉት በሐኪም ወርቅነህና በአቶ መላኩ በያን ስም የተቋቋመው ማህበር፤ ለዚህ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለው እንደሚያስቡም ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሊሰራ ለታቀደውና እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ የታሰበው ኢትዮ አሜሪካን ዶክተርስ ስኩል በርካታ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሲኤምሲ አካባቢ ሊገነባ ለታቀደው ለዚህ ሆስፒታል ህንጻ ማሰሪያ የሚሆን ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙና ቦታው እንደተሰጣቸው ግንባታውን በፍጥነት ለመጀመር መዘጋጀታቸውንም ዶ/ር ፋሲል በዚሁ ወቅት ገልፀዋል፡፡ “በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች ወደ አገራቸው መምጣትና ወገኖቻቸውን በሙያቸው ማገልገል የሁልጊዜም ህልማቸው ቢሆንም በጤናው ዘርፍ ያለው አገልግሎት አስተማማኝ ባለመሆኑ ብንታመምስ፣ ችግር ቢፈጠርስ? የሚል ስጋት አላቸው፡፡ እኔ ወደ አገሬ ለመመለስ መወሰኔን የነገርኳቸው በርካታ ጓደኞቼ “አብደሀል እንዴ?” ሲሉ ጠይቀውኝ ነበር፡፡ “አላበድኩም፤ ያበድኩት እዚህ በመኖሬ ነው” የሚል ምላሽ ሰጠኋቸው፡፡ መጥተሸ እስከምታይው ድረስ ማመን አትችይም፤ ሁሉም ነገር ያስፈራሻል፡፡ እኔም ሁለት ሶስት ጊዜ ተመላልሼ ካየሁ በኋላ ነው የወሰንኩት፡፡ አሁን በቋሚነት ኑሮዬን በአገሬ አድርጌ፣ ወገኖቼን ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ ተመልሻለሁ፡፡ አንዳንድ ማጠናቀቅ የሚገቡኝ ጉዳዮች ስለአሉ ለትንሽ ጊዜ መመላለሴ አይቀርም፡፡ ግን ሙሉ ጊዜዬን በአገሬ እየሰራሁ ለማሳለፍ ወስኜ ተመልሻለሁ፡፡ አሁን እንደኔ በርካታ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል - ዶ/ር ፋሲል፡፡ በንግድ ሚኒስትሩ አቶ አሊ ሲራጅ ተመርቆ የተከፈተው ዋሽንግተን ሜዲካል ሴንተር፤ በስፔሻላይዝድ ሐኪሞች የሃያ አራት ሰዓት የህክምና አገልግሎት  እንደሚሰጥም በምረቃው ስነስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡ በዚሁ የህክምና ማዕከል ምረቃ ላይ የተገኙ እንግዶች በሰጡት አስተያየት፤ የማዕከሉ መከፈት በህክምናው ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው ብለዋል፡፡  

Published in ዋናው ጤና

የአሜሪ ካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የሴቶችን የግብርና ምርቶች ተጠቃሚነትን ለማሳደግና አገራዊና ዓለማቀፋዊ ግብይታቸውን ለማሻሻል በዘረጋው ዩኤስኤአይዲ ኤጂፒ አምድ ፕሮግራሙ በተለያዩ ዘርፎች (በእቅድ አዘገጃጀት ቢዝነስ ፕላን፣ ሂሳብ አያያዝ፣ ቢዝነስ አመራር፣ …) ለ6 ወር ያሠለጠናቸውን ሴቶች ሸለመ፡፡ እንዲሁም ብዙ ሴቶችን በአባልነት የያዙ ዩኒዬኖችና ገበሬ ማኅበራት ከሽልማቱ ተቋድሰዋል፡፡
ቀዳማይ እመቤት ሮማን ተስፋዬና የአሜሪካ አምባሳደር በተገኙበት በዚህ ሳምንት በሂልተን ሆቴል በተካሄደው የሽልማት ሥነ - ሥርዓት፣ ከአዲስ አበባ፣ ከትግራይ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎች የተመረጡ 100 ሴቶች፣ ወደየመጡበት ሲመለሱ፣ እያንዳንዳቸው፣ ከሥልጠናው ያገኙትን እውቀትና ልምድ ለአምስት አምስት ሴቶች ለማካፈል ወይም ለማሠልጠን ቃል ገብተዋል፡፡
የዚህ ፕሮግራም ዓላማ በግብርና ዘርፎ የተሰማሩ ሴቶችን በማሠልጠን ችግሮቻቸውን በመቅረፍ ተሳትፎአቸው ማሳደግ ነው ያሉት በፕሮግራሙ የአግሮቢዝነስና ዲቨሎፕመንት ም/የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ታደለ ገላን፤ ሴቶቹ በቡና፣ በሰሊጥ፣ በስንዴ፣ በበቆሎ፣ በማር፣ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና የእሴት ሰንሰለት ለመጨመር፣ የገንዘብ ችግር ላለባቸው የብድር አቅርቦት በማመቻቸት፣ በየተሰማሩበት ፈጠራ ያሳዩትን በማበረታታት፣ የአመጋገብ (ኑትሪሽን) ሥርዓትን በማሳደግ፣ የባህርይ ለውጥ እንዲያደርጉና የመግባባት ችሎታቸውን ለማሻሻል ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ከአዲስ አበባና ከአራቱ ክልሎች በስልጠናው የተሳተፉ ሴቶች በተማሩት መሰረት ራሳቸው ባዘጋጁት ቢዝነስ ፕላን ተወዳድረው ያሸነፉ 5 ሴቶች፣ ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን አንደኛ የወጣችው ለቢዝነስ ስራዋ የሚያግዝ መሳሪያ መግዣ 200 ሺህ ብር ተሸልማለች፡፡ 2ኛ የወጣችው 150 ሺህ ብር፣ 3ኛ 100 ሺህ ብር፣ 4ኛ 75 ሺህ ብርና 5ኛ የወጣችው 50 ሺህ ብር ተሸልማለች፡፡  
በዚሁ ወቅት የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሺያ ሃስላክ ባደረጉት ንግግር፣ በእርሻው ዘርፍ ማለትም ቡና፣ ሰሊጥ፣ በቆሎ፣… ወደ ውጭ በመላክ የወንዶች ተሳትፎ በጐላበትና ተፅዕኖው በበዛበት ማኅበረሰብ ውስጥ፣ ነጋዴ የሆናችሁና የእርሻ ምርት ወደ ውጭ የምትልኩ አብዛኞቹ ሴቶች፣ በጣም ጠንካራና ደፋር ናችሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ተንሰራፍቶ ያለውን ሁኔታ በመጋፈጣችሁ በእርሻው አመራር ትክክለኛው አርአያና ሞዴል ናቸው፡፡ ዛሬ በቢዝነስ አመራር ፕሮግራም ለመሳተፍ ላደረጋችሁት ቁርጠኝነት እውቅና የምንሰጥበት ቀን ነው ብለዋል፡፡
ከዩኒየኖች መካከል ከፍተኛውን የሴት አባላት ቁጥርና ስም በተሰጠው ፎርም ከወረዳው ሴቶች መካከል 25 በመቶ መዝግቦ በማቅረብ 1ኛ የሆነው በደቡብ ክልል የየም ልዩ ወረዳ ተባበር ሁለገብ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒዬን ሲሆን፤ በዱባይ በተዘጋጀው የገልፍ 2015 ዓለም አቀፍ የንግድ ግብይት ላይ የኤክስፖርት ምርቱን እንዲያስተዋውቅና የንግድ ትስስር እንዲፈጥር ሙሉ ወጪው እንደሚሸፈንለት ታውቋል፡፡
ከደቡብ፣ ከትግራይ፣ ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች 1ኛ እና 2ኛ የሆኑት የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ እያንዳንዳቸው በእጅ የሚገፋ ትራክተር፣ 3ኛ እና 4ኛ የወጡት እያንዳንዳቸው ሞተር ቢስክሌት የተሸለሙ ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ 8ሺህ አዲስ የሴት አባላት እያንዳንዳቸው የአንገት ሻርፕ፣ አምስትና ከዚያ በላይ ሴቶች እንዲመዘገቡ ያደረጉ 500 ሰዎች እያንዳንዳቸው አንድ ዣንጥላ ተሸልመዋል፡፡

300 ዓመት ዕድሜ ያለው የጀርመኑ ባባሪያ 40 በመቶ ድርሻ አለው
ሀበሻ ቢራ፣ የፋብሪካው ግንባታና የመሳሪያዎች ተከላ 99 በመቶ ተጠናቆ፣ ኢንጂነሮች አንዳንድ የማጣሪያ ሥራ እያከናወኑ ስለሆነ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ገበያ እንደሚገባ የፋብሪካው ኮሜርሻል ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ዓለሙ አስታወቁ፡፡
አቶ ዮናስ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ከጀርመን፣ ከቼኮዝሎቫኪያ፣ ከሆላንድ፣ ከቻይናና ከኢትዮጵያ የተውጣጡ ኢንጂነሮች፣ አንዳንድ የማጣሪያና የለቀማ ሥራ እያጠናቀቁ ስለሆነ፣ ከማጣራቱ ሂደት በኋላ ቢራ እየተጠመቀ ሙከራ (ፍተሻ) ከተደረገ በኋላ ምርት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡
ሥራ ሲጀምር የፋብሪካው የማምረት አቅም በዓመት 30 ሚሊዮን ሊትር ወይም 300 ሺህ ሄክቶ ሊትር እንደሆነ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ፋብሪካው ተጨማሪ ማስተካከያ ተደርጎለት በዓመት 500ሺህ ሄክቶ ሊትር ቢራ እንደሚያመርት፣ አብዛኛው መሳሪያ KRONS ከተባለ የጀርመን ኩባንያ፣ ጋኖቹ ከቻይና፣ ሌሎች መሳሪያዎች ደግሞ ከዴንማርክና ከስዊድን መገዛታቸውን አስታውቀዋል፡፡
እኛ የቢራ ፋብሪካ ለማቋቋም ስንነሳ፣ በኢትዮጵያ ያለው የቢራ ኢንዱስትሪ ሁኔታ ተቀየረ፡፡ በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩ የቢራ ፋብሪካዎች በሙሉ ለግል የቢራ ኢንዱስትሪዎች ተሸጡና በዓለም ታዋቂ የሆኑ የቢራ ፋብሪካዎች ወደ ኢትዮጵያ ገቡ ያሉት አቶ ዮናስ፤ በኢትዮጵያ በነበረው የቢራ የፋብሪካ ማስተዳደር አቅም (ማኔጅመንት) በዓለም ታዋቂ፣ ከፍተኛ ልምድና እውቀት ካላቸው የቢራ ፋብሪካዎች ጋር መወዳደር ስለማይችል በቢራ ፕሮጀክት አስተዳደር፣ በቢራ ገበያ፣ በገበያና ልማት ስራ፣ …የሚያግዛቸው፣ በሽርክና አብሯቸው የሚሰራ ስትራቴጂክ አጋር መፈለጋቸውን፣ በዚሁ መሰረት፣ በአውሮፓ ከ300 ዓመት በላይ ዕድሜ ካለው ባባሪያ  ጋር ለመስራት ወስነው፣ የሀበሻ ቢራ ባለአክሲዮኖችም ይሁንታ እንደሰጧቸው አስረድተዋል፡፡
አቶ ዮናስ ለምን የጀርመኑን ባባሪያ እንደመረጡ ሲያስረዱ፤ ባባሪያውያን፣ በአገራቸው በአንድ ቦታ ላይ ብቻ በዓመት 600 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር የሚያመርት ፋብሪካ አላቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች አንድ ፋብሪካ እንዴት በዘመናዊ መንገድ መመራት እንዳለበት ያውቃሉ፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን ጠንካራ በሆነው የአውሮፓ ውድድር ከዓመት ዓመት እየተሻሻሉና እያደጉ 300 ዓመት መዝለቃቸው ነው፡፡ ባባሪያ የቤተሰብ ድርጅት ሲሆን አሁን ድርጅቱን እየመራ ያለው 7ኛ ትውልድ ነው ብለዋል፡፡
ባባሪያ በ17 ሚሊዮን ዩሮ፣ 40 በመቶ አክሲዮን ገዝቶ ከሃበሻ ቢራ ጋር በሽርክና በቅርበት እየሰራ ስለሆነ እውቀትና ልምዳቸው ወደ አገራችን ገብቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በሰራተኛ ቅጥርና ስልጠና በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን፣ በእነሱ አማካይነት 10 ሰራተኞች ወደ ሆላንድ ተልከውና ሰልጥነው መጥተው በፕሮጀክት ተከላና ጠመቃ እየተሳተፉ መሆኑን፣ ከማርኬቲንግ ክፍልም 5 ሰራተኞች ወደ ውጭ ተልከው የሽያጭ፣ የገበያና ልማት ስራ ተከታትለው መመለሳቸውን  ተናግረዋል፡፡
የገበያ ልማትና ሽያጩን በተመለከተ ባባሪያ ከ10 አገራት በላይ ቢራ ኤክስፖርት ስለሚያደርግ፣ ቢራ መጥመቅ ብቻ ሳይሆን መሸጡንም ያውቅበታል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በእውቀትና ልምድ ሽግግር፣ በስልጠና፣ በቢራ ፋብሪካ አስተዳደር፣ በቢራ ሽያጭ፣ በገበያ ልማት ስራ ከፍተኛ እገዛ እያደረገልን ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በቢራ ገበያ ያለው ውድድር ጠንካራ ስለሆነ እንዴት ወደገበያው ለመግባት እንዳሰቡ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው የነፃ የንግድ ውድድር ያለው በቢራው ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ውድድር ውስጥ ማነው የሚዘልቀው? የሚለው፣ የገበያውን ሁኔታና የደንበኛውን ስሜት በትክክል እያጠና የተጠቃሚው ወዳጅ የሆነ ደንበኛው የሚፈልገውን አገልግሎት አሟልቶ የሚያቀርብ፣ ሰራተኞቹ በባለቤትነት ስሜት የሚሰሩ፣ ሙያዊ ብቃት፣ ጥራት ያለውና አስደሳች አገልግሎት የሚሰጡ ሰራተኞች ያሉት ድርጅት እንደሆነ፣ ገልጸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ፣ በፋብሪካው ውስጥ ብክነትን የሚቀንስ ወጪ ቆጣቢ ሥርዓት ስለዘረጋን፣ በዘመናዊ መንገድ ጥራት ያለው ምርት ስለምናቀርብ፣ ከሁሉም በላይ ሰራተኞቻችን ከፋብሪካው አክሲዮን እንዲገዙ ዕድሉ ስለተሰጣቸውና በባለቤትነት ስሜት ስለሚሰሩ፣ በአሸናፊነት ገበያው ውስጥ እንቆያለን የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት በቢራው ዘርፍ ነፃ የገበያ ውድድር የሚባል ነገር አልነበረም ያሉት አቶ ዮናስ፤ አንድ ፋብሪካ በግሉ ወይም ፋብሪካዎች ተሰብስው ዋጋ የመጨመር ሁኔታ፣ አንዱ የሌላውን ዋጋ እየተከተለና በመገናኛ ብዙሃን (ቲቪ፣ ራዲዮና ጋዜጦች) በማስታወቂያ ጋጋታ ህዝቡን ግራ ያጋቡና ያዋክቡ ነበር ብለዋል፡፡ ዋልያ ቢራ ወደ  ገበያ ከመግባቱ ሁለት ወር በፊት ዋጋ እንዲቀንሱ ሲጠየቁ “አያዋጣንም” ያሉ ፋብሪካዎች፣ በየምርቶቻቸው ላይ የዋጋ ቅናሽ አድርገዋል፡፡ እያንዳንዱ ፋብሪካ የሚከተለው የራሱ የዋጋ ፖሊሲ አለው፡፡ እኛም  በራሳችን መንገድ ትክክለኛ ነው፣ የህዝቡን አቅም ያገናዘበና በተወዳዳሪነት ገበያው ውስጥ ሊያቆየን ይችላል የምንለውን ዋጋ ይዘን እንቀርባለን ብለዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ ዮናስ ወደ ገበያ እንገባለን ብለው ያቀዱት በሚያዝያ 2014 ቢሆንም ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮች፣ ለምሳሌ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ብድር ማጣት፣ በ2010 ዓ.ም የተደረገው የዶላር ዋጋ ቅነሳ፣ ባለአክሲዮኖች የሚፈለግባቸውን ገንዘብ በወቅቱ ያለመክፈል፣ … የፋብሪካውን ግንባታ እንዳጓተቱት ጠቅሰው፣ ባለአክሲዮኖች በትዕግስት በመጠበቃቸው አመስግነው አሁን ወደ ገበያ ልንገባ ስለሆነ ደስ ብሎናል፤ ደስ ይበላችሁ ብለዋል፡፡


Saturday, 24 January 2015 12:51

የፖለቲካ ጥግ

ፖለቲካ፤ ለፖለቲከኞች ሊተው የማይችል ትልቅ ቁምነገር ነው     ወደሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ፡፡
ቻርልስ ደጐል
* በዲሞክራሲ ሥርዓት አንደኛው ፓርቲ ሁልጊዜ ዋና ጉልበቱን     የሚያውለው ሌላኛው ፓርቲ አገር ለመምራት ብቁ አለመሆኑን     ለማረጋገጥ በመሞከር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሁለቱም ይሳካላቸዋል፡፡ ደግሞም     ትክክል ናቸው፡፡
ኤች ኤል ሜንኬን
* ዲሞክራሲ በመጠኑ የምትጠላውን     እጩ እንድትመርጥ የሚፈቅድልህ ሥርዓት ነው፡፡
ሮበርት ባይርኔ
* ፖለቲከኞችና ዲያፐር (የሽንት ሁለቱም በተመሳሳይ ምክንያት በየጊዜው መለወጥ አለባቸው፡፡
ያልታወቀ ፀሐፊ
* ፖለቲከኛ ነገ፣ በሚቀጥለውሳምንት፣ በሚቀጥለው   ወር፣ በሚቀጥለው ዓመት የሚከሰተውን ነገር የመተንበይ ችሎታ ያስፈልገዋል፡ከዚያም በኋላ ያልተከሰተበትን ምክንያት የማስረዳት ችሎታ ሊኖረው ይገባል፡፡
ዊንስተን ቸርችል
* የፖለቲካ ቀልድ ችግሩ፣ የቀለድንባቸው ፖለቲከኞች መመረጣቸው ነው፡፡
ያልታወቀ ግለሰብ
* ፖለቲካ፤ ውሳኔዎች አስፈላጊነታቸው እስኪያበቃ ድረስ የማቆየት ጥበብ     ነው፡፡
ሔንሪ ኪውይሌ
* ልታሳምናቸው ካልቻልክ አደናግራቸው፡፡
ሃሪ ኤስ ትሩማን
* ሰላማዊ ትግል እውን እንዳይሆን የሚያሰናክሉ፣ የትጥቅ ትግልን አይቀሬ ያደርጉታል፡፡
ጆን ኤፍ ኬኔዲ
* ፖለቲካ እጅግ ውድ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሳ ለመሸነፍ እንኳን ብዙ ገንዘብ ይፈልጋል፡፡
ዊል ሮጀርስ

*  ፋና “ድምጽ ለተነፈጉ ተቃዋሚዎች ድምጻቸው ነኝ” ብሏል  
*  “ፈንድ” አፈላልጌ  የፓርቲዎች ክርክር ለማዘጋጀት አስቤአለሁ   
*  “ሳይማሩ ያስተማሩኝን መምህሮቼን አመሰግናለሁ” ከማለት ያድነን!  

    በአንድ የአገራችን ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን መፅሄት ላይ አንዱ ተመራቂ ከፎቶው ስር ምን ብሎ እንደጻፈ ታውቃላችሁ? “ሳይማሩ ያስተማሩኝን መምህራኖቼን አመሰግናለሁ” (ምኑን ተማረው ታዲያ!) የሚገርምም፣ የሚያሳዝንም፣ የሚያስቆጭም መልዕክት ነው፡፡ በደጉ ጊዜ “ሳይማር ያስተማረኝን ወገኔን…” ሲባል ነበር የምናውቀው፡፡ (ሳይማሩ የሚያስተምሩ መምህራን ግን ይደንቃሉ?!)
አሁን በቀጥታ ወደ ምርጫ ወጐች እንግባ፡፡  ባይገርማችሁ… ከምርጫ ጋር በርቀትና በቅርበት የተያያዙ ውዝግቦች አሁንም ቀጥለዋል፡፡ (የአውጉቾ ተረፈን “እያስመዘገብኩ ነው” የሚል አጭር ልብወለድ አንብባችኋል?)
እኔ የምላችሁ---ባለፈው ሳምንት ምሽት ሬዲዮ ፋና፤ የአንድነትን ሁለት የተለያዩ አመራሮች ያወያየበትን መንገድ ታዝባችሁልኛል? እኔማ ጋዜጠኛው የቱ ጋ መቆም እንደፈለገ ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡ (መሃል አልነበረማ!) ባለፈው ሳምንት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በምርጫ ዙሪያው በሸራተን ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ግን አንድ ነገር ፍንትው አለልኝ - በአስማት እንዳይመስላችሁ፡፡ የኮርፖሬሽኑ ተወካዮች በአንደበታቸው ከተናገሩት ነው፡፡ አዎ --- ድምፅ ላጡ ድምፅ እንሆናለን ነው ያለው፡፡ (በሬዲዮ ክርክሩ ጋዜጠኛው የቱ ጋ እንደቆመ የገባኝ ይሄኔ ነው!)
 ትንሽ ግልጽ ያልሆነልኝ ምን መሰላችሁ? ፋና፤ ድምፅ ላጡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ድምፅ መሆን የጀመረው በዘንድሮ ምርጫ ነው ወይስ ጥንትም ባህሉ ነበር? (እንዴት ሳንሰማ ቀረን ብዬ እኮ ነው!)  ለነገሩ ጥንት ባህሉ ሆነም አልሆነም ለውጥ የለውም፡፡ የሚመዘነው በዛሬ ሥራው ነው፡፡ እናም  ድምጽ አጥቷል (መድረክ ልትሉትም ትችላላችሁ!) ላለው የአንድነት ክፋይ ፓርቲ አመራር፣ ከመቅጽበት ደርሶላቸዋል፤ በብርሃን ፍጥነት እኮ ነው!  ቡድኑ በጥር 3 ላይ በዲአፍሪክ ሆቴል ጉባኤ ጠርቶ፣የፓርቲው ህጋዊ ፕሬዚዳንት መሆኑን አሳወቀ፤ ፋናም ታዲያ በዚሁ ወር ነው ቡድኑ ድምጽ አልባ መሆኑን ተረድቶ “ድምጽ እሆነዋለሁ” ያለው (ተሳሳትኩ እንዴ?) እናንተ ግርም እኮ ነው የሚለው? (ግጥጥሞሹን ማለቴ ነው!) ከመቼው የአመራር ቡድኑ ተፈጥሮ፣ ከዚያ ድምጽ ተነፍጎት፣ ከመቼው ፋና ድምጽ እንደሆነው---ትንግርት ነው!
በነገራችን ላይ የውስጥ ችግራቸውን ለመፍታት ተስኗቸዋል የተባሉት አንጋፋዎቹ አንድነትና መኢአድ (አሁንም በዝና አንጋፋ ናቸው ብዬ እኮ ነው?!) የምርጫውን አጀንዳ ጠለፉት አይደል? አያችሁልኝ--- ኋላ ቀር አስተሳሰብ ይዞ ቶሎ ቶሎ መራመድ እንደማይቻል? ራሳቸውን ችለው ሳይሆን እኛንም ይዘውን እኮ ነው የተጎተቱት? በእነሱ የውስጥ ችግር የተነሳ፣ ሁላችንም እኮ ስለ ምርጫው ሳይሆን የፓርቲው ህጋዊና ፎርጂድ  አመራር የቱ ይሆን በሚል ምናባዊ ደመና ላይ መንሳፈፍ ይዘናል፡
 በጣሙን የሚገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? የስልጣን ጥማት ያለበት ሰው፤ በአንዲት ጀንበር አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መስርቶ ፕሬዚዳንት መሆን እየቻለ፣ (እንደ ግል ኩባንያ መቁጠር ችግር አምጥቷል!) ምንድነው አንድ ፓርቲ ላይ ሙዝዝ ማለት፡፡ የአንድነት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው፤ በ“ዳያስፖራ ጫና” ከሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ የተመረጠው አመራር ህገወጥ ነው በሚል የሚከስሰው ድምፅ አልባ የተባለው የአቶ አወል ቡድን፤ ራሱን የፓርቲው አመራር አድርጐ ለመሰየም እኮ አፍታ አልወሰደበትም፡፡ (አመቺ ጊዜ ሲጠባበቅ የነበረ አይመስልም!)
እኔ የምለው ግን ድምፅ ተነፍጓል የተባለው ይሄ ቡድንስ፣ ህጋዊነቱን የሚያረጋግጥልን ማነው? (ወይ እች አገር አሉ አቦይ!) ለካስ የመንግስት ብቻ ሳይሆን  የፓርቲ ስልጣንም እንዲህ ያናክሳል? (በአንድ ስሙ የመንግስት ስልጣን ቢሆን እኮ ይሻል ነበር?!)
በነገራችን ላይ የአቶ አወል ቡድን፤ ኢንጂነሩ የዳያስፖራ ተፅእኖ አላሰራኝም ብለው በለቀቁበት ሁኔታ ብሄራዊ ም/ቤቱ አዲስ ፕሬዚዳንት መምረጡ ትክክል አይደለም በሚል ሲሟገት በEBC ተመልክተናል፡፡(የኢንጂነሩን ወደ ስልጣን መመለስ የሚፈልግ ይመስላል አይደል?) ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ አሁን በሆነ ተአምር (ለምሳሌ ውዝግቡን ለመፍታት በሚል!) ኢንጂነር ግዛቸው ወደ ቀድሞ የፕሬዚዳንትነት ስልጣኔ እመለሳለሁ ቢሉ፣ እሺ የሚላቸው አያገኙም፡፡ እንደውም ያን ጊዜ ሁለቱ የፓርቲውን መዘውር የጨበጡ ተፃራሪ ቡድኖች ግንባር ፈጥረው፣ ኢንጂነሩን የሚታገሏቸው ይመስለኛል (የፓርቲ ስልጣን ብርቅ ሆኗል ስላችሁ!)
የዘንድሮ ምርጫን አስመልክቶ ለተቃዋሚዎች የወጣላቸውን አዲስ ስም ሰምታችሁልኛል? - “ጐምዢው” ፓርቲዎች ተብለዋል፡፡ (ኮፒራይቱ የማን እንደሆነ አልተረጋገጠም!) አዎ ገዢው ፓርቲና “ጐምዢው ፓርቲ” ናቸው እንግዲህ በ2007 አገራዊ ምርጫ ላይ የሚወዳደሩት፡፡ በእስካሁኑ አካሄድ ግን መኢአድና አንድነት ጐምዢው ፓርቲዎች ለመባል እንኳን የሚበቁ አይመስሉም፡፡ በምርጫው መሳተፍ ካልቻሉ እንዴት ሊጐመዡ ይችላሉ? ጐምዢ እኮ የተባሉት የመንግስት ስልጣን ፍለጋ ለምርጫ ተወዳድረው፣ ድሉን ገዢው ፓርቲ ስለሚጠቀልለው ነው (የማሸነፍ ምስጢሩ ገና አልገባቸውም!)
ሰሞኑን አንዳንድ የEBC “የአዲስ አበባ ነዋሪዎች”፤ እነመኢአድን በተመለከተ የሚሰጡትን አስተያየት እየሰማችሁ ነው፡፡ “ቤታቸውን ሳያፀዱ…” እያሉ ቆዩና አንድ ቀን ድንገት “በእነሱ የተነሳ ደም መፋሰስ እንዳይከሰት…” ምናምን የሚል “አሸባሪ አስተያየት” መሰንዘር ጀመሩ፡፡ የኢቢሲ ኤዲተር ዘገነነው መሰለኝ  አልተደገመም፡፡ እንዴ --- የኢቢሲ “አንዳንድ ነዋሪዎች” አበዱ እንዴ?  በሰላም አገር--- የምን ደም መፋሰስ ነው የሚያወሩት?
ከምሬ ነው የምላችሁ --- አንዳንድ “የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” ባይሆኑ ኖሮ፣ “የሌለ ሽብር በመፍጠር የህዝብን ሰላም ለማወክ ተንቀሳቅሰዋል” ተብለው ፍርድ ቤት ይገተሩ ነበር፡፡ በደህና ጊዜ ወደ “አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች” ጎራ መግባታቸው ጠቀማቸው፡፡ የእነሱን “አሸባሪ አስተያየት” ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ለ90ሚ. ህዝብ ያሰራጨውም EBC ሆነ እንጂ ጣቢያው ተዘግቶ ክስ ይመሰረትበት ነበር፡፡ እሱ እንኳን ቢቀር ጉደኛ ዶክመንተሪ ይጠናቀርበት ነበር - “ጨለምተኛና ብጥብጥ ናፋቂ” በሚል፡፡ (EBC የቤት ልጅ መሆኑ አተረፈው!) በነገራችን ላይ ይሄ ምርጫ ከመድረሱ በፊት ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲቀጥል----እኔም የዜግነቴን ለማበርከት ስለምፈልግ፣ ፈንድ ወይም ስፖንሰር በማፈላለግ ላይ እገኛለሁ፡፡ ሃሳቤ ምን መሰላችሁ? (አይዲያዋን ለመመንተፍ እንዳትሞክሩ!)  ወዳጆቼ፤ሪስኪ ፕሮጀክት እኮ ነው፡፡ ይሄውላችሁ ---- ደህና ፈንድ ሰብሰብ አደርግና፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ጉደኛ ዲቤት አዘጋጃለሁ፡፡ (እስክጨርስ ካልተከፋፈሉ ነው እንግዲህ!) በዚህ ዘርፍ በቂ ልምድ ስለሌለኝ፣ በቀደም በሸራተን ተመሳሳይ ጉባኤ ያዘጋጀው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከልምዱ እንዲያካፍለኝ ደጅ እጠናና ወደ ሥራው መግባት ነው፡፡ እኔ ግን እንደምታውቁት መስዋዕትነት---በጎ ፈቃደኝነት ወዘተ-- ምናምን አላውቅም፡፡ ትርፍና ኪሳራውን አስልቼ ነው የምገባበት፡፡ አገር የተጎዳችው፣ ፓርቲዎች ስልጡን የፖለቲካ ባህል ያልፈጠሩት -- ትርፍና ኪሳራውን ሳያሰሉ በጭፍን እየገቡበት እኮ ነው፡፡ እናላችሁ---የምርጫ ክርክር ማዘጋጀትም ቢሆን ለእኔ ቢዝነስ ነው፡፡ ዋናው ነገር ፓርቲዎቹ እኔ ከማሰናደው ነገር መጠቀማቸው ነው፡፡ እነሱ ከተጠቀሙ ደግሞ እኔም መጠቀም አለብኝ፡፡ ይሄን ሁሉ የምዘባርቀው እኮ ወደጄ አይደለም፡፡ ፋና የሸራተኑን ጉባኤ ቤሳ ቤስቲን ሳያገኝ፣ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበት በሚል በነጻ አዘጋጅቶት ይሆናል በሚል ሰግቼ ነው፡፡ (እሱ ኮርፖሬሽን፤ እኔ ግለሰብ!)   በነገራችን ላይ ፕሮጀክቱ ከተሳካልኝ፣ የክርክሩ ጊዜያዊ ርዕስ “ምርጫ 2007ና ስልጡን ፖለቲካ--” የሚል ነው፡፡ መቼም ለፋና ተፈቅዶ ለእኛ ሲሆን አይቻልም ቢባል “ፌር” አይሆንም፡፡
 ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ… የበቀደሙን የፋና ጉባኤ ረግጠው የወጡት የአንድነቱ አቶ አስራት ጣሴ ኮርፖሬሽኑን ይቅርታ ጠይቁ ሊባሉ እንደሚችሉ ጠርጥሬአለሁ፡፡ “ዎክ አውት አድርገዋላ!” ቆይ ግን ባላመንኩበት ጉባኤ የመሰብሰብ ግዴታ አለብኝ እንዴ? አንቀጽ 39 በጸደቀበት አገር ባትፈልግም መቀመጥ አለብህ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ተገቢ አይደለም ብቻ ሳይሆን አምባገነንነትም ጭምር ነው፡፡ ይልቅስ አንድ ሃሳብ አለኝ፡፡ የፓርቲ አመራር ውይይት ረግጦ በወጣ ቁጥርና ጥፋት በፈጸመ ጊዜ ሁሉ ይቅርታ ጠይቅ፣ አልጠይቅም የሚል ውዝግብ ውስጥ ከመግባት፣ ለምን የይቅርታ ሥነምግባር ደንብ ተረቅቆ ፓርቲዎች አይፈራሩም? (አደራ! ዋናውንም ያልፈረሙ አሉ ብላችሁ ሃሳቤን ውድቅ እንዳታደርጉብኝ!) ከተሳካ እኮ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ዓለምም ጥሩ ተመክሮ ይሆናል፡፡
ይሄ እንዳለ ሆኖም  ከየአቅጣጫው የ2007 ምርጫን  ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ--ለማድረግ --- ሁሉም ሲረባረብ ማየት በጣም ያስደስታል፡፡ (“የማይተማመኑ ባልንጀሮች በየወንዙ ይማማላሉ” እንዳይሆን ግን ጠንቀቅ ነው!) ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ?  እንደ 97 ምርጫ “እንከን የለሽ” ምናምን አለማለት ነው፡፡ እሱ እኮ ነው ጉድ የሰራን፡፡ እንከን የለሽ ምርጫ እንኳንስ በዲሞክራሲ ዳዴ ላይ ላለነው ለእኛ ቀርቶ ዲሞክራሲን ከእናት ጡት ጋር ለሚጋቱትም አልተሳካም፡፡ እንከን የለሽ ምርጫ በዓለም ላይ እውን የሚሆነው መቼ መሰላችሁ? የሮቦት ዘመን ሲመጣ ነው፡፡ (የሰው ልጅማ ፍጹም አይደለም!)  
እናላችሁ-- መራጩ - ሮቦት፣ ምርጫ ቦርዱ - ሮቦት፣ የድምጽ ታዛቢው- ሮቦት፣ ድምጽ ቆጣሪው- ሮቦት፣ አሸናፊው- ሮቦት፣ ተሸናፊውም- ሮቦት ሲሆኑ ብቻ ነው እንከን የለሽ ምርጫ የሚሳካው፡፡ እኛ ደግሞ  የሮቦት ዘመንን አንሻም፡፡ (እንከን የለሽ ምርጫ ይቅርብን እንጂ!)
ትዝ ይላችሁ እንደሆነ --- የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ (መሬት ይቅለላቸውና!) መንግስት የመላዕክት ስብስብ አይደለም ብለው ነበር፡፡ ለመንግስት ብቻ ሳይሆን ለህዝብም፣ ለፓርቲዎችም---የሚሰራ አባባል ነው፡፡ እንከን የለሽነት ወይም ፍጹምነት ከመላዕክት ወገን እንጂ ከሰው ልጅ አይደለም፡፡ እንዲያም ሆኖ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ ግን እንችላለን - ከፈለግንና ከጣርን፡፡ ሌላ እኮ አይደለም የሚያስፈልገን - ትንሽ ሰልጠን ማለት ብቻ ነው፡፡ ሥልጣኔም እንደ ዲሞክራሲ በአንድ ጀንበር የሚመጣ ግን አይደለም፤ ሂደት ነው፡፡ የሚያስፈልገንም በየ5 ዓመቱ  ምርጫ ሲመጣ ብቻ አይደለም፡፡ በአዘቦት ቀን ህይወታችንም ከስልጣኔ ጋር መተዋወቅ ይኖርብናል፡፡ በ11ኛው ሰዓት የተከሰተው የመኢአድና የአንድነት ፓርቲዎች ክፍፍል እኮ ሌላ ሳይሆን የዚህ ስልጣኔ አለመዳበር ነው፡፡ የስልጡን ፖለቲካ ባህል ድህነት! በሰላሙ ጊዜ ልዩነትን በስልጡን መንገድ ተከባብሮ በመወያየት፣ ችግርን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመፍታት እየተለማመዱ ቢቆዩ እኮ ይሄ ሁሉ ግርግር ባልተፈጠረ ነበር፡፡
የጦቢያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ስልጡንነት ብዙ እንደሚቀራቸው ትንሽ ማሳያ ላቅርብና ልጨርስ፡፡ ገዢውንም “ጎምዢውንም” ፓርቲዎች ይመለከታል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በየአጋጣሚው የሚያወጡትን መግለጫ አይታችሁልኛል? (ውበትም ይዘትም የላቸውም እኮ!) ገዢው ፓርቲ በአብዛኛው የሚያወጣው መግለጫ፣ የሰላም ጊዜ ሳይሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው የሚመስለው፡፡ የሌለ ጠላት ፈጥሮ ሲያወግዝ ይገኛል፡፡ የ“ጎምዢዎቹ” ፓርቲዎች ግን ይብሳል፡፡ ሁሌም መግለጫቸው በስድብና በውግዘት የታጀበ ነው፡፡ ሰነፍ የጻፈው መግለጫ ነው የሚመስለው፡፡ የቋንቋ ውበት ቢኖረው ደግሞ ለሥነጽሁፍ ዋጋው ተብሎ ሊነበብ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳልኳችሁ---  ውበትም ይዘትም የለውም፡፡ ይሄም የኋላቀርነት መገለጫ እንጂ የሥልጣኔ አይደለም፡፡ እናም ሥልጣኔው ይሄን ሁሉ ስለሚጨምር ብዙ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ የማይቻል ግን አይደለም፡፡
 በመጨረሻ፤ ምርጫው በልምዳችንም ሆነ ከሌላው ዓለም በቀመርነው ተመክሮ ወይም በጸሎትም ይሁን በአስማት ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዓለም የሚተርፍ ተመክሮ ባይገኝበት እንኳን ለራሳችን የምንማርበት እናድርገው፡፡
“ሳይማሩ ያስተማሩኝን መምህራኖቼን አመሰግናለሁ” ከማለት ይሰውረን!!  


Saturday, 24 January 2015 12:47

አስገራሚ የቃላት ፍቺዎች

ተሞክሮ
 ሰዎች ለስህተታቸው የሚሰጡት ስም
አቶሚክ ቦምብ
 ሁሉንም ፈጠራዎች የሚያወድም ፈጠራ
አድርባይ
ድንገት ወንዝ ውስጥ ቢገባ ገላውን መታጠብ የሚጀምር ሰው
ወንጀለኛ  
ከመያዙ በቀር ከሌላው ሰው የማይለይ
ሃኪም
 በሽታህን በክኒን ገድሎልህ፣ አንተን በክፍያ የሚገድልህ ሰው
አለቃ
 ስትዘገይ ቀድሞህ የሚገባ፣ ስትቀድም የሚዘገይ
ኮሚቴ  
በግላቸው ምንም መስራት የማይችሉ ሰዎች በጋራ ምንም መስራት እንደማይቻል ለመወሰን በአንድ ላይ የሚቀመጡበት
ክላሲክ
ሰዎች የሚያወድሱት ግን የማያነቡት መፅሃፍ
የጉባኤ አዳራሽ
 ሁሉም ሰው የሚናገርበት፣ ማንም የማያዳምጥበትና በመጨረሻም ሁሉም የማይስማሙበት ስፍራ
ተስፈኛ
 ከአይፍል ማማ ላይ እየወደቀ ሳለ መሃል ላይ “አያችሁ ገና አልተጎዳሁም” የሚል ሰው
ስስታም
ሃብታም ሆኖ ለመሞት በድህነት የሚማቅቅ ሰው
ፈላስፋ
ሲሞት እንዲወራለት በህይወት ሳለ ራሱን የሚያሰቃይ ጅል
ወዘተ
ሌሎች በትክክል ከምታውቀው በላይ ታውቃለህ ብለው እንዲያምኑ ማድረጊያ ዘዴ

Published in ጥበብ
Page 6 of 18