Saturday, 17 January 2015 11:00

‘ኒው ወርልድ ኦርደር’

እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ የሚሏት ነገር አለች፡፡ ያው እንግዲህ ‘ዕጣ ፈንታችንን የሚወስኑልን’ እንደመሰላቸው ሲያሽከረክሩን… አለ አይደል… መሽከርከር ነው፡፡ አሁን፣ አሁንማ እንትን ከተማ ሲያነጥሱ እንትን ከተማ የጉንፋን ወረረሽኝ የሚገባባት ዘመን ነው፡፡ ምን የማይደገስልን ነገር አለ፡፡
እናላችሁ…‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ የሚሏትን ነገር በብዙ ነገሮች ውስጥ ብልጭ ያደርጓታል፡፡ ነገርዬው… አለ አይደል… ‘የነበረው እንዳልነበረ’ አይነት ነው፡፡
ለምሳሌ ‘ቦተሊካ’ን ውሰዱት፡፡ (እንግዲህ አየሩ እንደዛ መሽተት ጀምሮ የለ!) እናላችሁ…ለስንትና ስንት ዓመት “ዓይንህ ለአፈር…” ሲባባሉ ይከርማሉ፡፡ እርስ በእርስ መወነጃጀል የ‘ቦተሊካ’ ‘ፍሬሽማን ኮርስ’ ነገር የሆነ ይመስል ….አሁንማ የእርግማን መአት መስማቱን እኛም ለመድነው፡፡ እኔ የምለው…ግርም አይላችሁም! ‘ቦለቲከኞቹ’ … አለ አይደል… “እኛ ከእናንተ የተሻለ ሀሳብ አለን…” ከመባባል ይልቅ… “እናንተ እኮ እንዲህ እንዲህ ለማድረግ ስውር ዓላማ ያላችሁ…” …ምናምን መባባል የሚያቆሙት መቼ ነው? አሰኝቷችሁ አያውቅም!
ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…እኛን የእንትና ደጋፊ፣ የእንትና ተላላኪ ምናምን አስብለው የጎሪጥ መተያያት ከጀመርን በኋላ እነሱ በጎን ገጥመው ቁጭ! የእኔ ቢጤው ደግሞ ወዳጆቹን አጥቶ ቁጭ!
“እንዲህ ተጠማምደው ድንገት ፊት ለፊት ቢገናኙ ምን ይሆኑ ይሆን!…” ተብሎ የሚሰጋላቸው ሰዎች ምን ቢሆኑ ጥሩ ነው…..‘አዲስ’ ፍቅር ይጀምራሉ፡፡
ምን አለፋችሁ… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ አይነት ነገር ሆኖ ቁጭ!
ከዛማ ምን አለፋችሁ…ነገርዬው “አዲስ ፍቅር ይዞኛል…” ይሆንና እኛ “ጉርምርሜ…” ስንባል “ያሆ በሌ!” ስንል የከረምነው አጨብጭበን ቁጭ፡፡
እናማ… “እንዲህ ዞረው እንትን ለእንትን ለሚገጥሙት እኛን ለምን ያቆራርጡናል!” ብለን ለአንድዬ ‘እናሳጣቸዋለን’፡፡ ይህ ነገር ለእኛ ነው ጎበዝ ጠንቀቅ በል… ሲባባሉ “እነኚህ ሰዎች ‘ተላለቁ’…” ስንል እነሱ ግን ትከሻ ለትከሻ ገጥመው በብሉ ሌብል ምናምን ‘ይለቃለቃሉ’!
ነገርዬው… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ አይነት ነዋ!
እኔ የምለው ዞረው ሊገጥሙ የእርግማኑ፣ የዘለፋው መአት ምንድነው፡፡ (ሀሳብ አለን… አንዳንድ ወንበር ላይ ያላችሁ ሰዎች፣ እባካችሁ ቋንቋችሁን ኤዲት አድርጉልን፡፡ አሀ… ለነእንትና የታሰበው ‘ሞራል መስበሪያ’ እኛንም ጨረፍ ሊያደርግ ይቻላላ!)
ታላቁ መጽሐፍ… “ሳውል፣ መመለስህ ላይቀር ለምን ትረግጠኛለህ?” ይላል፡፡ እናማ መመለሳችሁ ላይቀር እርስ በእርስ አትረጋገጡማ! ለእኛም አትትረፉን!! ቂ…ቂ….ቂ…
ደግሞላችሁ…እንትናዬን እንደ እንትና…አለ አይደል… ለዓይኗ የሚያስጠላት ነገር የለም፡፡ …እንደሚባለው “ዓለም ላይ የሚቀረው የመጨረሻ ወንድ ቢሆን እንኳን ዘወር ብዬ አላየውም…” ምናምን የምትል አይነት ነች፡፡ “አሁን ይሄንንም የምታገባ ሚስት ትኖር ይሆናል እኮ!” ምናምን እያለች ስታንቋሽሸው ትኖራለች፡፡
ድንገትላችሁ….ነገሩ ሁሉ ይገለበጥና በየት ይገናኙ በየት አንድዬ ይወቀው … ተጣብቀው ቁጭ! እሷ ባማችው ቁጥር እኮ እናንተ ስንትና ስንት ‘አሜንድመንት’ ጨምራችሁበታል!
እሱን ስታይ መንገድ እንዳልተሻገረች ሁሉ… አለ አይደል….አንድ ቀን ሳይደውል ካለፈ አገር ምድሩ ይደበላለቃል፡፡
ነገርዬው… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ አይነት ነዋ!
ይቺን ስሙኝማ… እሱዬው እናት አባቷ ሳያዩ በድብቅ በእሷ ፈቃደኝነት ጠልፏት ሊሄድ የቤተሰቡ ደንበኛ የሆነ ባለታክሲን ይጠራዋል፡፡ ሁለቱ መኪና ውስጥ እንደ ገቡም እሱዬው… “ከከተማ ለመውጣት ምን ያህል ታስከፍለናለህ?” ይለዋል፡፡
ባለታክሲውም “ግዴለም፣ ምንም አላስከፍላችሁም…” ይለዋል፡ እሱዬው ግራ ይገባውና “ሥራ አይደለም እንዴ! ለምንድነው የማታስከፍለን?” ይለዋል፡፡ ባለታክሲ ምን ቢል ጥሩ ነው... “አባቷ አስቀድመው ከፍለውኛል፡፡” አሪፍ አይደል! ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ይላችኋል እንዲህ ነው፡፡
የገዛ ልጁን ጠለፋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስፖንሰር የሚያደርግ ስንትና ስንት አባት ይኖራል!
የአባትነት ሚና ‘ማሻሻያዎች’ ተደርገውበታላ!
‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ነዋ!
እናላችሁ… “እንደው ባል እንኳን ባይመጣላት ለወጉ እንኳን ጠልፏት የሚሄድ ሰው ይጥፋ!”  የሚሉ ወላጆች ቢኖሩ አይገርምም፡፡
የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የወላጅ ሚና እኮ ተገለባብጦ… አለ አይደል… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ አይነት ነገር ሆኗል፡፡
እናላችሁ… ለአስተማሪዎች “እባካችሁ ልጄ አጉል ነገር እንዳትለምድ፣ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር እንዳትውል ተከታተሉልኝ…” የሚሉ ወላጆች ‘ዝርያቸው’ ለመጥፋት ተቃርቧል፡፡
 ልክ ነዋ…“ልጄን ተቆጣህብኝ…! ብሎ እንትንዬውን ከጎኑ ‘ላጥ’ አድርጎ አስተማሪው ግንባር ላይ የሚደግን ‘አባት’ አለበት የሚባልበት አገር ነው እኮ! የአሥራ ምናምን ዓመት ልጇ ሲጋራ ስታጨስ በመያዟ የተጠራች ‘እናት’… “እኔ አስተምሩልኝ እንጂ ሲጋራ ታጭስ አታጭስ ተከታተሉልኝ አልኩ!”  ወይ… የምትልበት አገር ሆኗል ይባላል፡፡
‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ነዋ!
እሷዬዋ እጮኛዋን ከቤተሰቦቿ ጋር ታስተዋውቀዋለች፡፡ አባቷ ስለ እሱ የበለጠ ለማወቅ ወደ አንድ ክፍል ይወስደዋል፡፡ የልጅቱ አባት የናጠጠ ሀብታም ነበር፡፡
“እሺ፣ እቅዶችህ ምንድናቸው?”
“የኃይማኖት ምሁር ነኝ፡፡”
“በጣም ጥሩ ነው፣” አለ አባትየው፡፡ “ግን ልጄ ጥሩ ቤት እንድታገኝ ምን ለማድረግ አስበሀል?”
“እኔ ጥናቴን እቀጥላለሁ፣ እግዚአብሔርም ሁሉንም ነገር ያደርግልናል፡፡”
“መልካም፣ የጋብቻ ቀለበትስ እንዴት እድርገህ ነው ልትገዛላት ያሰብከው?”
“እኔ ጥናቴን እቀጥላለሁ፣ እግዚአብሔርም ሁሉንም ነገር ያደርግልናል፡፡”
“ስለ ልጆችስ ምን ታስባለህ?” አለ አባትየው፡፡ “ልጆችህን በምን መልክ ለማሳደግ ነው ያሰብከው?”
“አያስቡ፣ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ያደርግልናል፣” ሲል እጮኛ ሆዬ መለሰ፡፡
ውይይቱ በዚህ መልክ ቀጠለ፡፡ ሁለቱ እጮኛሞች ተሰናብተው ሲሄዱ እናትየው አባትየውን ስለ ልጃቸው እጮኛ ምን መረጃ እንዳገኘ ትጠይቀዋለች፡፡
አባትም ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…ሥራም ሆነ ዕቅዶች የሉትም፡፡ ግን ጥሩው ነገር ምን መሰለሽ፣ እኔ እግዚአብሔር መስየዋለሁ፡፡”  ቂ…ቂ…ቂ…
ዘንድሮ በእንትናዬ ሰልካካ አፍንጫ ሳይሆን በአባቷ ካዝና እየተማረከ አባወራ የሚሆን መአት ነው፡፡ እናማ…የአባት አንጀት አይጨክንም በማለት… “እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ያደርግልናል…” የካዝናውን ስፋትና ርዝመት እያሰበ ነው፡፡
‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ነዋ!
ስሙኝማ… የአባት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አባት ልጁ ስለ አልኮል መጠጥ መጥፎነት ሊያስረዳው እየሞከረ ነበር፡፡
እናማ…አንዲት ትል በንጹህ ውሀ ውስጥ፣ አንዲት ትል ደግሞ በውስኪ ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ ውሀ ውስጥ ያለችው ትል ምንም አትሆንም፡፡ ውስኪ ውስጥ የነበረችው ግን ተንፈራፍራ ሞተች፡፡
አባትዬውም ወደ ልጁ ዘወር አለና… “እሺ የእኔ ልጅ፣ አሁን ያየኸው ምንን ያሳያል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ልጅ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው….
“የሚያሳየውማ አልኮል ከጠጣህ ትላትሎቹ በሙሉ እንደሚሞቱ ነው፣” አለና አረፈው፡፡
‘የዘንድሮ ልጆች’ ከመቼው ነገር እንደሚይዙ የሚገርም ነው፡ እናማ…እንደ ድሮው በሎሊፖፕና በደስታ ከረሜላ የሚታለል ልጅ ያለበት ዘመን እያለፈ መሆኑን ልብ ማለት ነው፡፡
‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ነዋ!
ብቻ…ለበጎም ይሁን ለክፉ… ብዙ ነገሮች እየተለዋወጡ መሆኑን ማወቅ ደግ ነው፡፡ የዚሀ አገር አንድ ትልቅ ችግር የሚመስለኝ ዘመን፣ ከዘመን ጋርም የሰዉ አመለካከትና አስተሳሰብ እየተለወጠ መሆኑን ነገሬ አለማለታችን፣ ወይም ‘ነገሬ ለማለት’ ፈቃደኛ አለመሆናችን ይመስለኛል፡
ለደግ፣ ለደጉ… ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ ያምጣልን!
መልካም የጥምቀት በዓል!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Published in ባህል

እሑድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም ማለዳ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቤተኛና ወዳጆች ለሆኑ የውጪ ሀገር ዜጎችም ጭምር መልካም ረፋድ አልነበረም፡፡ አሳዛኙ ዜና የብዙዎችን ጆሮ ለማዳረስና ለማሳዘን ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ “ቀደምቱና ታሪካዊው የጣይቱ ሆቴል በእሳት ተቃጠለ!” ይህንን ዜና በርካታ ድረ ገጾችና መገናኛ ብዙሀን ተቀባበሉት፡፡ ክስተቱ እጅጉን አሳዛኝ ነበርና የምር ኢትዮጵያዊነት ለሚሰማውና እሴቶቹን ለሚያከብር ዜጋ ሁሉ ሀዘኑ መሪር ነበር፡፡
                 “የሰማይ አሞራ ልጠይቅሽ ወሬ
                 ተቃጥሎአል መሰለኝ ሸተተኝ ሀገሬ”  (ዮፍታሄ ንጉሴ)
እንዳለመታደል ሆኖ እንደ ህዝብ የራሳችን ለሆኑ ነገሮች ያለን ግምት እጅጉን ያነሰ ነው፡፡ እናም የእኛ ከሆኑ ነገሮች ይልቅ የሌሎችን እናከብራለን፡፡ በዚህም ታሪካችንን፣ እውነታችንን… በአጠቃላይ ማንነታችንን ቀርሰው የያዙ በርካታ እሴቶቻችንን ቸል እንላለን፡፡ ብለናልም! አስገራሚው ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህን ችላ ብለናቸው የኖርነውን እሴቶቻችንን የምናከብረው ባዕዳን ሲመሰክሩላቸው ስንሰማ ወይንም እሴቶቹን በአንዳች ያልተጠበቀ አደጋ ስናጣቸው ነው፡፡ ያኔ ወጋችን ሁሉ እነሱን ይሆናል፡፡ ሲያልፍ ልንዘነጋቸው፡፡ ወረተኞች ነን ልበል?!
“(እቴጌ) ጣይቱ ሆቴል” በሀገራችን ቀዳሚው ሆቴል መሆኑን በርካታ ድርሳናት መዝግበዋል፡፡ ሆቴሉ በ1898 ዓ.ም በነሀሴ ወር ግንባታው ተጀምሮ በ1900 ዓ.ም ጥቅምት 25 ቀን ተመርቆ መከፈቱን ታላቁ ብዕረኛ ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለውና የአጼ ምኒልክን ታሪክና ተግባራት በከተበበት መጽሐፉ ይገልጻል፡፡
በዘመኑ በነበረው ባህልና ማህበረሰባዊ አስተሳሰቦች ምክንያት በወቅቱ ሆቴል ከፍቶ “ምግብ ከፍላችሁ ተመገቡ፤ መጠጥም እንዲሁ” ማለት፣ እንዲሁም ሆቴሉ እንኳን ቢገኝ ከፍሎ መመገብ እንደነውር የሚታይ በመሆኑ፣ ህዝቡም ሆነ መኳንንቱ ስለማይፈጽሙት ጉዳዩ ንጉሡን አጼ ምኒልክንም ሆነ እቴጌ ጣይቱን እጅጉን አሳስቧቸው ነበር፡፡ እናም ምኒልክና ጣይቱ ይህንን መፈጸም ነውር እንዳልሆነ በቅርባቸው ላሉ መኳንንት ከማስረዳት ባለፈ በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ ነባሩን ባህልና ልማድ ባጠበቀ ማህበረሰብ ውስጥ አዲስ ባህልን መትከል ቀላል አይደለምና፡፡ የጳውሎስ ትረካ ይህን ይላል፡-
 “እንደ አገር አባባል ጣይቱ እጅ የሚያስቆረጥም ወጥ እያሠሩ ገበያ ቢጠብቁ ጠፋ:: እንኳን ምግብ መብላት ከግሪኮች ሻይ ቤት ገብቶ ሻይ መጠጣት ነውር ነበረና ጣይቱ ጠዋት የሚያሠሩት ወጥ ለሠራተኞቹ የማታ ራት ይሆን ጀመር፡፡ የሚስታቸው ገበያ ማጣት ያሳሰባቸው አጤ ምኒልክ አንድ ቀን ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በአካባቢያቸው ላሉ መኩዋንንቶች “ጣይቱ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ከፍታለችና ኑ እንሂድና ልጋብዛችሁ” ብለው ወሰዱዋቸው፡፡ መኳንንት በላ ጠጣና ምኒልክ 30 ብር ከፈሉ፡፡
በማግሥቱ እንደተለመደው ገበያ ቢጠበቅ ጠፋ ቀጥሎም ጠፋ፤ ቀጥሎም ጠፋ፡፡ እንደገና ምኒልክ ሆቴል ገብቶ መብላት ነውር ያለ መሆኑን ለመኳንንቱ ገልፀው እንደገና ምሣ ጋበዙ፡፡ በሌላው ቀን አሁንም ገበያ አልተገኘም፡፡ ቢጠበቅ ቢጠበቅ ድርሽ የሚል ሰው ጠፋ፡፡
በሌላ ቀን ደግሞ አጤ ምኒልክ ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በዙሪያቸው ላሉ መኳንንት “ሰማችሁ ወዳጆቼ” አሉ:: “በፈረንጅ አገር አንድ ቀን አንድ ሰው የጋበዘ እንደሆነ ያ የተጋበዘ ሰው በሌላ ቀን ደግሞ ብድሩን ይከፍላል ብድሩን ካልከፈለ ግን እንደ ነውር ይቆጠርበታል፡፡” ብለው ንግግራቸውን ሳይጨርሱ መኳንንቱ “እርስዎን ፈርተንና አፍረን ነው እንጂ የሚሆንልን ከሆነ የምኒልክን ብድር ለመመለስ እኔ አለሁ” እያለ ተራ በተራ ከሆቴል ቤት ምኒልክንና ጣይቱን ይጋብዝ ጀመረ፡፡ ገበያ እየደራ ሄደ፡፡ ምሳችንን እቴጌ ሆቴል ሄደን እንብላ የሚለው ስለበዛም ስሙ እቴጌ ሆቴል ተባለ፡፡”
ይህንን ታሪክ መዝግቦ ላቆየልን ለደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ “እረፍት ይስጥልን!” ብለን እንቀጥል፡፡ እንግዲህ ጣይቱ ሆቴል ተመርቆ ሥራ የጀመረበትን ጊዜ ይዘን ስናሰላ እነሆ ሆቴሉ የ107 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ነው ማለት ነው፡፡ ሊያውም አምስት ዘመነ መንግስታትን ያሳለፈ ትልቅ ቅርስ! በሆቴሉ ነገሥታቱንና ቤተሰቦቻቸውን ወዳጆቻቸውን ጋብዘዋል፤ እርስበርስም ተገባብዘዋል፡፡ መኳንንቱ የሚወዱትን ጨብጠው ብዙ አውግተዋል፡፡ የበርካታ የውጪ ሀገር መሪዎችም አርፈውበታል፡፡  ጣይቱ ሆቴል በሀገራችን የሆቴልና ቱሪዝም መስክ ቀዳሚው በመሆኑና አንድ ለእናቱ ሆኖ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱም ጭምር በውስጡ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ተወስተውበታል፤ ተወስነውበታልም፡፡ ሆቴሉ ለዘመናት የሰጠው አገልግሎትና ያቀፋቸው ትዝታዎች፣ በዚህም የተሸከመው ታሪክ የትየለሌ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጣይቱ ሆቴል ከተለመደው የሆቴል አገልግሎት ባለፈ የብዙ ጥበባት ቤትና ልዩ ልዩ ድርጊቶች መከወኛም ነበር፡፡ የማይሰለቸውና የማይታጎለው የኢትዮጵያ ጃዝ ሙዚቃ መገኛና ማቀንቀኛ፣ የበርካታ ፊልሞችና መጻሕፍት መመረቂያ፣ የበርካታ ጥበባዊ ክንውኖች “ማሄጃ” ነበር፡፡ እጅጉን ለፒያሳ ቅርብ በመሆኔ በሳምንት ውስጥ ጣይቱ ሆቴልን የማላይባቸው ቀናት ጥቂት ናቸው፡፡ በሆቴሉ ውብ አዳራሽ በተካሄዱ ልዩ ልዩ ጥበባዊና ሌሎች ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ላይ ታድሜአለሁ፡፡ ትዝታዬ ብዙ ነው! መቃጠሉን ስሰማ ያ ግርማ ሞገሱ የሚጣራው ህንፃና በውስጡ ያቀፋቸው የማይተኩ ቅርሶች፣ እንዲሁም ውብ አዳራሹና የታደምኩባቸው ፕሮግራሞች በአይኔ ሞሉ፡፡ ራሱ ህንፃውና አቅፎአቸው የኖሩት ቅርሶች የማንነታችን አንድ ምስክር፣ የታሪካችን መዛግብት ናቸው፡፡ እንዴት እንተካቸው ይሆን? እውነት ለመናገር በሆቴሉ ግድግዳ ላይ የተሰቀሉት ፎቶ ግራፎች፣ መገልገያ ቁሶች፣ ህንፃውን ቀጥ አድርገው የተሸከሙት ዋልታዎች… ዙሪያ ገባውን ሁሉ ደጋግሜ ያየሁት ቢሆንም ወደ ሆቴሉ በገባው ቁጥር ይህ ውበት እንደ አዲስ ትኩረቴን ይስባል፡፡ ዙሪያ ገባው ኢትዮጵያዊነትን ይናገራል!
ይህንን እጅጉን የማንነታችንና የታሪካችን ምስክር የሆነን ህንፃና ጓዞቹን በአደጋ አጣን፡፡ (“መንግስት አደጋው በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡” ቢልም፡፡ ለነገሩ ሌላስ ምን ሊል ይችላል?!) ጉዳቱ በቀደምት አበው የተሰሩ ታሪካዊ ቅርሶችን በማሳጣት ብቻ እንዳላበቃና በዛሬው ትውልድ የተበጁ ልዩ ልዩ እሴቶችንም እንደነጠቀን እየተነገረ ነው፡፡ የምር ታሪካችንን ለምናከብርና የኢትዮጵያ አክባሪ ለሆኑ የውጪ ወዳጆችን ሁሉ ሀዘኑ ታላቅ ነው! መጽናናቱን ይስጠን ከማለት ሌላ  እንግዲህ ምን እንላለን? አላውቅም!
በመጨረሻም አንድ እጅጉን ያስገረመኝንና እሱን ተከትሎ በውስጤ የተነሳውን ጥያቄ አንስቼ ላብቃ፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካን መንግስት አምባሳደር የሆኑት ፓትሪሺያ ሃስላክ በጣይቱ ሆቴል ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን በራሳቸውና በአሜሪካ ህዝብ ስም የገለጹበትን የሀዘን መልዕክት አነበብኩ፡፡ ከአምባሳደሯ መልዕክት ጀርባ ያለውን የዲፕሎማሲ ጣጣ ትተን እናስብ፡፡ መገረማችን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ይህንን ተከትለው የሚመጡ በርካታ ጥያቄዎች አሉና፡፡
ለምንም ይሁን፣ ሌላ መንግስት ስለደረሰብን ጉዳት ሀዘኑን ሲገልጽ የቅርሱና የታሪኩ ባለቤት የሆነው መንግስት በጠፋው ጉዳት የምር ምን ተሰምቶት ይሆን? ፕሮግራሞችን በመደጋገም የአየር ሰዓታቸውን የሚሸፍኑት የመንግስት መገናኛ ብዙሀንስ (ከዜና ሽፋን ባለፈ) ለክስተቱ የሰጡት ሽፋን ምን ይመስል ነበር?... “ባለቤቱ ያቃለለውን አሞሌ…!” ይመስላል፡፡  
ሌላም ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ በጣይቱ ሆቴል የተነሳውን የእሳት አደጋ በቁጥጥር ሥር በማዋል ታላቁን ቅርስ ለማዳንስ ምን ያህል ጥረት ተደርጎ ይሆን? “የእሳት አደጋ በደረሰ ቁጥር በፍጥነት ደርሶ የሚጠበቅበትን አገልግሎት አልሰጠም” እየተባለ ሠርክ ወቀሳ የሚደርስበትና እዚያው መሀል ፒያሳ ላይ የሚገኘው ተቋምስ አደጋውን ለመቆጣጠር የሚጠበቅበትን ያህል ደክሞ ይሆን? ሌላም ብዙ!
በአደጋው የደከሙባቸውን ንብረቶቻቸውን ላጡ ተቋማትና ግለሰቦች፣ ለሆቴሉ ቤተኞች፣  በተለይም የማንነቱ ምስክርና ታሪክ የሆነውን ቅርስ ላጣው ኢትዮጵያዊ ሁሉ መጽናናትን ተመኘሁ!!
መልካም ሰንበት!!


Saturday, 17 January 2015 10:55

በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ

ዋጋ በመወደዱ የኢቢሲ ቀጥታ ስርጭት አጠያያቂ ሆኗል
አልጄርያ ፤ጋና፤ ካሜሮን፤ ኮትዲቯርና ደቡብ አፍሪካ ተጠብቀዋል
የአውሮፓ ክለቦች 30 ምርጥ አፍሪካውያን በማጣት ለ1 ወር ይቃወሳሉ
ተጨዋቾቹ በ60 አገራት የሚጫወቱና እስከ 701 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋ ያላቸው ናቸው


30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  በምድብ 1 የሚገኙት አዘጋጇ ኢኳቶርያል ጊኒ ከኮንጎ ኪንሻሳ በሚያደርጉት ጨዋታ 35700 ተመልካች በሚያስተናግደው ባቱ ስታድዬም  ዛሬ ይጀመራል፡፡ ኢኳቶርያል ጊኒ 30ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት የበቃችው በኢቦላ ስጋት መስተንግዶዋን የሰረዘችውን ሞሮኮን በመተካት ሲሆን ከ3 ዓመት በፊት ከጋቦን ጋር በጥምረት ያዘጋጀችውን 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫን ልምድ በመንተራስ መስተንግዶውን ውጤታማ ለማድረግ ትፈልጋለች፡፡ በአጠቃላይ የአፍሪካ ዋንጫውን በኢኳቶርያል ጊኒ አራት ከተሞች የሚገኙት 4 ስታድዬሞች ያስተናግዷቸዋል፡፡ አራቱ ስታድዬሞች ለ1 ወር በሚቆየው ውድድር ከ200ሺ በላይ ተመልካች እንደሚያስተናግዱ የሚጠበቅ ሲሆን አንዱን ጨዋታ በአማካይ ከ28ሺ በላይ ተመልካች ስታድዬም ተገኝቶ እንደሚመለከተው ተገምቷል፡፡
በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የቀጥታ ስርጭት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ስለናረ 30ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ማስተላለፍ እንደማይችል አስታውቋል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ውድድሩን በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለማስተላለፍ  ለተለያዩ አገሮች የማሰራጫ ጣቢያዎች ፈቃድ የሰጠ ሲሆን የአፍሪካ ዋንጫን ከመሰረቱት አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ እንደተለመደው በቀጥታ ስርጭት ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ በሚጠየቀው ውድ ክፍያ ሳቢያ ተቸግራለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቀጥታ ስርጭት የአፍሪካ ዋንጫውን ለማስተላለፍ በድርድር ላይ ሲሆን በካፍ ፍቃድ አግኝተው የስርጭት መብት ከያዙት የፈረንሳዩ ስፖርት 5 ሚዲያና የኒውዘርላንዱ ኤል ሲቱ ሚዲያ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ እና እስከ 3.8 ሚሊዮን ብር እንደቅደምተከተላቸው መጠየቃቸውን ዘገባዎች አውስተዋል፡፡
በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሚሳተፉት 16 ብሄራዊ ቡድኖች እስከ 368 ተጨዋቾች የተመዘገቡ ሲሆን በ60 የዓለም አገራት በሚገኙ ክለቦች እና የሊግ ውድድሮቻቸው የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ክለብ ልምድ ያላቸውና የዋጋ ግምታቸው ከ701 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚተመን ነው፡፡ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት ግን የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎችና ክለቦቻቸው እስከ 30 የሚደርሱ ወሳኝ ተጨዋቾችን  ለ1 ወር በማጣት ይቃወሳሉ፡፡ በተለይ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግና የፈረንሳይ ሊግ 1 ዋና ተጎጂዎቹ ናቸው፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከ12 ክለቦች የተውጣጡ  19 ተጨዋቾች በአፍሪካ ዋንጫው ቢያንስ ለሶስት ሳምንታት ማጣቱ የማይቀር ሲሆን ሁኔታው በአንዳንድ ክለቦች ከፍተኛ የውጤት ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በአንድ ሳምንት ጨዋታዎች ከሚገቡት ጎሎች 50 በመቶውን የሚያስቆጥሩት አፍሪካውያን ተጨዋቾች በመሆናቸው ነው፡፡ 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሚካሄድበት የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለብሄራዊ በድናቸው የተጠሩ አፍሪካውያን ተጨዋቾች ቢያንስ ሶስት የፕሪሚዬር ሊግ እና አንድ የኤፍኤካፕ ጨዋታ ያመልጣቸዋል፡፡
ይህ ሁኔታም ፕሪሚዬር ሊጉ በጎል ድርቅ እንዲመታና አንዳንድ ክለቦች በደረጃቸው እንዲዋዥቁ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡  ከጋናና ኮትዲቯር ከእያንዳንዳቸው 4፤ ከአልጄርያ ፤ ከሴኔጋል እና ከኮንጎ ከእያንዳንዳቸው 3  እንዲሁም ከኮንጎ ኪንሻሳ፤ ከኢኳቶርያል ጊኒና ከማሊ ከእያንዳንዳቸው ቢያንስ 1 ተጨዋች በአፍሪካ ዋንጫ  እንደሚሰለፉ ታውቋል፡፡ በተለይ ከምርጥ ተጨዋቾች ማንችስተር ሲቲ ኮትዲቯራዊውን ያያ ቱሬ፤ ዌስትሃም ዩናይትድ ሴኔጋላዊውን ዲያፍራ ሳካሆ፤ ኒውካስትል ዩናይትድ ሴኔጋላዊውን ፓፓ ሲሴ፤ ክሪስታል ፓለስ የኮንጎውን ያኒክ ቦላሴ ማጣታቸው በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡
በሌላ በኩል የአፍሪካ ዋንጫው በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ለሚገኙ ክለቦች የተጨዋቾች መመልመልያ ዋንኛ መድረክ ይሆናል፡፡ የቤልጅዬም፤ የሆላንድ፤ የጀርመንና የፈረንሳይ ክለቦች በርካታ ወጣት የአፍሪካ ተጨዋቾችን ለማግኘት ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጡ በመገለፅ ላይ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተለያዩ ምክንያቶች ሌሎች ትልልቅ ተጨዋቾችንም አንመለከትበትም፡፡ የሴኔጋሉ ዴምባ ባ፤ የካሜሮኑ አሌክስ ሶንግ፤ የጋናዎቹ ኬቨን ፕሪንስ ቦአቴንግና ሱሊ ሙንታሪ ባለመመረጣቸው እንዲሁም እነ ዲዲዬር ድሮግባ እና ሳሙኤል ኤቶ በጡረታ ከየብሄራዊ ቡድኖቻቸው በመሰናበታቸው አናያቸውም፡፡
በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከሚሳተፉት 16 ብሄራዊ ቡድኖች አልጄርያ ፤ጋና፤ ካሜሮን፤ ኮትዲቯርና ደቡብ አፍሪካ ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ናቸው፡፡ የምእራብ አፍሪካዎቹ ጋና ለ30 ዓመታት ኮትዲቯር ደግሞ ለ20 ዓመታት ከዋንጫው በመራቃቸው ዘንድሮ ድሉን ለማጣጣም መቻላቸው ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ለአራት ጊዜያት የአፍሪካ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው የምእራብ አፍሪካዋ ካሜሮንና ምንም እንኳን ለዋንጫው በከፍተኛ ልምድና ውጤት ተጠቅሳለች፡፡  16 ብሄራዊ ቡድኖች ከተደለደሉባቸው አራት ምድቦች የሞት ምድብ የተባለው ምድብ 3 ሲሆን ምናልባትም የውድድሩ አሸናፊ ሊወጣበት እንደሚችል ይጠበቃል፡፡  ሻምፒዮኑ በካፍ የሚቀርብለት የገንዘብ ሽልማት 1.5 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡
አልጄርያ 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለ16ኛ ጊዜ ተሳታፊ የምትሆንበት ነው፡፡ ፈረንሳዊው የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ክርስትያን ጉርኩፍ ለዋንጫው ድል የተሰጠውን ግምት በተመለከተ ሲናገሩ ምርጥ ስብስብ ቢኖረንም፤ ዋንጫውን ማሸነፍ እንደምንችል የተገለፁ በርካታ ትንበያዎችን ሳንሰማ እና ከልክ ባለፈ መተማመን ሳንዘናጋ ስኬታማ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን አስቀድሞ በተሳተፋባቸው 15 የአፍሪካ ዋንጫዎች 1 ጊዜ ሻምፒዮን (1990)፤ 1 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ(1980)፤ 2 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃ (1984, 1988)እንዲሁም 2 ጊዜ አራተኛ ደረጃ(1982, 2010) ነበረው፡፡
በበርካታ ቅድመ ትንተናዎች እና ዘገባዎች ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድል ከፍተኛ ግምት የወሰደው የጋና ብሄራዊ ቡድን ነው፡፡ በቀድሞ የቼልሲ አሰልጣኝ እስራኤላዊው አቭራም ግራንት የሚመራው የጋና ብሄራዊ ቡድን ዘንድሮ በአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፈው ለ20ኛ ጊዜ ይሆናል፡፡ ጋና ባለፉት 19 የአፍሪካ ዋንጫዎች በነበራት የተሳትፎ ታሪኳ 4 ጊዜ ሻምፒዮን (1963, 1965, 1978, 1982)፤ 4 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ(1968, 1970, 1992, 2010)፤ 1 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን (2008) እንዲሁም ለሶስት ጊዜያት በአራተኛ ደረጃ (1996, 2012, 2013) ጨርሳለች፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ በ18 ጎሎች  የምንግዜም ኮከብ ግብ አግቢ የሆነው ሳሙኤል  ኤቶን ያላካተተው የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን በጀርመናዊው አሰልጣኝ  ቮልከር ፊንኬ በመመራት ጠንካራ ተሳትፎ እንደሚያሳይ ይጠበቃል፡፡ ካሜሮን በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ 17ኛው ተሳትፎ ሲሆን  አስቀድሞ በተሳተፈችባቸው 16 የአፍሪካ ዋንጫዎች 4 ጊዜ ሻምፒዮን(1984, 1988, 2000, 2002)፤ 2 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ(1986, 2008)፤ 1 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃ (1972)እንዲሁም 1 ጊዜ አራተኛ ደረጃን (1992) በማግኘት ከፍተኛውን ልምድ አካብታለች፡፡
ለኮትዲቯር ወርቃማ የእግር ኳስ ትውልድ ውድድሩ ሻምፒዮን ለመሆን 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻው መጨረሻ እድል ሆኖ እየተገለፀ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ዝሆኖቹ በአምበላቸው ዲድዬር ድሮግባ እየተመሩ ለዋንጫ ከፍተኛ ግምት እየተሰጣቸው አልተሳካላቸውም፡፡ ኮትዲቯር  ባለፉት 20 የአፍሪካ ዋንጫዎች የተሳትፎ ታሪኳ 1 ጊዜ ሻምፒዮን(1992)፤ ሁለት ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ(2006, 2012)፤ 4 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃ (1965, 1968, 1986, 1994) እንዲሁም 2 ጊዜ አራተኛ ደረጃ (1970, 2008) አስመዝግባለች፡፡
ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የተደረገውን የምድብ ማጣርያ በማለፍ በውድድሩ ለዘጠነኛ ጊዜ የሚሳተፈው የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን በወጣት ተጨዋቾች ስብስቡ ለዋንጫ ግምት ማግኘቱ አስገራሚ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ባለፉት 8 የአፍሪካ ዋንጫዎች በነበራት የተሳትፎ ታሪኳ 1 ጊዜ ሻምፒዮን (1996)፤ 1 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ (1998) እንዲሁም  1 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃ ደረጃ (2000) አግኝታለች፡፡

የያኔውን የስልጣኔ ባህል የምናፈቅር፣ የያኔዎቹን የስልጣኔ ጀግኖች የምናከብር ከሆነ፣ ያወረሱንን ነገር የሙጢኝ ይዘን መቀመጥ ሳይሆን፣ በአርአያነታቸው ተነቃቅተን፣ የእውቀትና የፈጠራ ባህላቸውን በመከተል ገና ድሮ ድሮ፣ ከሸክላ ቴክኖሎጂ በተጨማሪ የብረትና የፕላስቲክ ቴክኖሎጂ መፈልሰፍ፣ ከጠላና ጠጅ አልፈን የወይን ጠጅና የቢራ ፋብሪካ መፍጠር በቻልን ነበር። ግን አላደረግነውም። የያኔው የስልጣኔ ባህል ተዘንግቶና ጠፍቶ፣ የስልጣኔ ቅርስና ቅሪት ብቻ ነው የተረፈን - እንስራና እንስሪት። ይሄ፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ የውድቀትና የኋላቀርነት አርማ ነው።
አሳዛኙ ነገር፤ ይህንን አርማ በማውለብለብ ከውድቀት የምንድን ይመስላቸዋል። የውድቀታችንን ምንነትና ሰበቦችን አልተገነዘብነውም ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው።

  • በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተመዘገቡ የስልጣኔ ቅኝቶች ከ15 እንደማይበልጡ ብዙ የታሪክ ምሁራን ይገልፃሉ። 7ቱ ጠፍተዋል። ከቀሪዎቹ መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ነው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ከአለም ልዩ ናት ይላሉ - ሳሙኤል ሃቲንግተን።
  • ነገር ግን፣ አገራችን ግን፤ “ልዩና ድንቅ” የሆነችበትን ምክንያት ብዙዎቻችን በቅጡ አናውቀውም። “ልዩና ድንቅ” የሆነችው፣ በጠላ እና በድፎ ዳቦ እየመሰለን፣ ቢራን እና ኬክን እንደ “ባህል ወረራ” ከቆጠርናቸው፤ የአገሪቱ የጥንት ስልጣኔና ታሪክ ባእድ ሆኖብናል ማለት ይቻላል።  

በጣይቱ ሆቴል ቃጠሎ ሰበብ የተፈጠረውን ንትርክ ስመለከት፣ ለገና በዓል በተዘጋጀው የቴሌቪዥን ፕሮግራም የአቶ ውብሸት ወርቃለማሁና የአቶ ዳንኤል ክብረት ንግግሮችን ስሰማ፣ “አቤት የዚህች አገር ሸክም መብዛቱ!” አሰኘኝ። ሁለቱ ታዋቂ ሰዎች፣ በ“ምዕራባዊያን ባህል” እንደተወረርንና የኢትዮጵያ ባሕል እንደተሸረሸረ በቁጭት እየተንገበገቡ ሲያማርሩ፣ ብዙ ታዳሚዎች በድጋፍ አጨብጭበዋል። በእርግጥ፣ ቁጭቱና ምሬቱ፣ “የገና ዛፍ” ላይ ያነጣጠረ መሆኑ አስገራሚ ነው።
ማለቴ... እጅጉን የሚያስቆጩ ስንትና ስንት ትልልቅ ጉዳዮች በተትረፈረፉባት አገር፣ በ“ገና ዛፍ” መንጨርጨርን ምን አመጣው? በሰው ልጅ ታሪክ ላይ በጣት ከሚቆጠሩ የስልጣኔ ማዕከላት መካከል አንዷ እንዳልነበረች፣ ባለፉት ሺ አመታት አንዳች ተጨማሪ እውቀትን፣ ሙያዊ ጥበብን፣ ብልፅግናንና የስኬት ሰብእናን መፍጠር ተስኗት፤ የጭፍን እምነት፣ የኋላቀር ልማድ፣ የድህነትና የሚስኪንነት መናሃሪያ ለመሆን የተዳረገች አገር ውስጥ ነው የምንኖረው። ከምር በዚህ እንቆጫለን? አይመስለኝም። እንዴት መሰላችሁ?
ከድህነትና ከረሃብ በመውጣት ኑሮን ማሻሻልና መበልፀግ ባለመቻላችን ሳይሆን፤ ረሃብተኛና ተመፅዋች መባላችን ሲቆረቁረን አስቡት። በየዓመቱ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች ተስፋ ቆርጠው እንዲሰደዱ የሚገፋፋ ከባድን ድህነትና ችግር ውስጥ መሆናችን ሳያሳስበን፤ ሳዑዲና ኩዌት ሄደው በግርድና መስራታቸው “የአገርን ገፅታ ያበላሻል” እያልን እንንጨረጨራለን። አይገርምም? የድሮውን የሚያሻሽል ነገር መስራትና መፍጠር አለመቻላችን ሳያስቆጨን፣ ሌሎች ሰዎች የፈጠሩትን ተውሰን በመጠቀማችን እርር ትክን እንላለን። በሌላ አነጋገር፣ ቅደመ አያቶች የፈጠሩትን አኗኗር ይዘን፣ ያንኑ እየደጋገምን፣ እዚያው በነበሩት ቦታ ቆመን መቅረት ነው የምንፈልገው። እና ይህንን ደግሞ፣ “ባህልን ማወቅ” “ባህልን ማክበር” ወይም “ባህልን መጠበቅ” ብለን እንጠራዋለን። በተቃራኒው፣ “ባህልን አለማወቅ”፣ “ባህልን ማርከስ” እና “ባህልን ማጥፋት” ብንለው ይሻላል።
እንደ ጥንቶቹ የስልጣኔ አያቶች፣ በእውቀት የመራቀቅ፣ በሙያዊ ጥበብ አዳዲስ የተሻለ ነገር የመፈልሰፍና የመስራት ባህል ቢኖረን ኖሮ፣ ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ እንዲያ አይነት ባህል እንዲኖረን የምንፈልግ፣ የምንሞክርና የምንጥር ቢሆን ኖሮ... ያኔ “ባህልን ማወቅ፣ ማክበርና መጠበቅ” ስንል ትክክለኛ ትርጉም ይኖረው ነበር። ግን፣ ከመነሻው የባህልን ምንነት ስላላወቅነው፤ ሸማ፣ የሳር ጎጆ፣ የበሬ እርሻ፣ እንስራ የመሳሰሉ... ከሺ ዘመናት በፊት በታላቅ የፈጠራ ባህል አማካኝነት የተፈለሰፉና ከትውልድ ትውልድ በልማድ የወረስናቸውን ነገሮች እንደታቀፍን ቆመን ስንቀርና ደንዝዘን ስንቀመጥ፣ የባህል ባለቤት የሆንን ይመስለናል። እነዚያ የፈጠራ ሰዎች፣ እንዲህ ሆነን ቢያዩን በጣም ነበር የሚያዝኑብን። ለምን በሉ።     
ከሺ ዓመታት በፊት የነበሩ የቀድሞ አያቶችኮ፣ ከትውልድ የወረሱትን ቅርስ ታቅፈው እዚያው እየረገጡ መቀመጥን የሚፀየፉ ስለነበሩ፣ የስልጣኔ ባህልን የሚያሰፍን የፈጠራና የስኬት ሰብዕናን የገነቡ አዋቂዎች፣ ጥበበኞችና ጀግኖች ስለነበሩ ነው፣ ድፎ ዳቦንና እንጀራን፣ ጠላንና ጠጅን፣ ማረሻንና ገንቦን፣ ሸማንና ስልቻን፣ ጎተራንና ጎጆን፣ ቤተመንግስትን እና የቀን መቁጠሪያን፣ ቋንቋንና ሰዋስውን፣ ፊደልንና ፅሁፍን፣ የአድናቆት ሃውልትንና ግጥምን፣ የሙዚቃ መሳሪያንና ዘፈንን... በአጠቃላይ የእውቀት አድማስን ለማስፋት፣ ኑሮን ለማበልፀግና የሕይወትን ጣፋጭነት ለማጣጣም የሚጠቅም ነገር ሲፈጥሩና ሲያሻሽሉ የኖሩት።
እኛ ግን፣ ከአላዋቂነታችን የተነሳ፣ የቅድመ አያቶች የፈጠራ ውጤቶችን ስናይ፣ ለምሳሌ የፊደልና የፅሁፍ ስልጣኔ ቀላል ሊመስለን ይችላል። የንግግር ድምፆችን የሚወክሉ ምልክቶችን መፍጠር በጣም ከፍተኛ እውቀትንና ጥረትን ስለሚጠይቅ፣ ብዙ ቋንቋዎች ፅሁፍ የላቸውም። እንደ እብራይስጥ በመሰሉ ፅሁፍ ያላቸው ቋንቋዎች እንኳ፣ “አናባቢዎችን” የሚወክል ምልክት መፍጠር አቀበት እንደሆነባቸው ምዕተ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሄ የመጨረሻው ቃል ያለ “አናባቢ” ሲፃፍ “ተቀጠረወለ” የሚል ይሆናል። “ቁጠር” እና “ቆጠሩ” የሚሉ ቃላት ያለ አናባቢ ብንፅፋቸው “ቀጠረ” በሚል በግርድፍ ስለሚቀሩ አንዱን ከሌላው መለየት አንችልም። የተሟላ የፊደልና የፅሁፍ ስርዓት መፍጠርን ትተን፣ የቁምነገሩን ክብደት የምትጠቁም ቀለል ያለች አንዲት ነጠላ ምሳሌ ልጥቀስላችሁ። ዛሬ በዘመናችን በርካታ የዚሁ ቋንቋ ምሁራን፣ “ቷ” የሚለው ፊደል፣ “ትዋ” ወይንም “ቱዋ” ከሚሉ ድምፆች የትኛውን እንደሚወክል ሲምታታባቸው ይታያል። ትክክለኛው “ትዋ” ነው።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ከማረሻና ከድፎ ዳቦ እስከ ፅሁፍና የመንግስት ስርዓት ድረስ፣ አንዳችም እንደ ዝናብ ከሰማይ የወረደ እውቀትና ጥበብ የለም። የስልጣኔ ባህልን የገነቡ አዋቂ የፈጠራ ሰዎች በየዘመናቸው በፈርቀዳጅነት ስለፈጠሩትና ስላሻሻሉት ነው እውን ሆኖ የምናየው። በአጭሩ፣ ፈር ቀዳጅ የፈጠራ ሰዎች ነበሩ። ምኒልክም በአቅማቸው፣ የመጀመሪያውን ዘመናዊ የሳይንስ ትምህርት ቤት፣ ጣይቱ የመጀመሪያውን ሆቴል የከፈቱትም በፈር ቀዳጅነት ነው። እኛ ግን፣ እንደነሱ አይነት የፈጠራና የስኬት ሰብዕና የተበራከተበት የስልጣኔ ባህል አልገነባንም፤ የግንባታ ጅምርም ሆነ ውጥን የለንም። ጨርሶ በሃሳባችን ውስጥ አይገባም። የቱን ያህል ብርቅና ድንቅ የስልጣኔ ባህል እንደቀረብን በቅጡ ባለመገንዘባችን አልያም የመገንዘብ ፍላጎት ስለሌለን፤ “ትልቅ ነገር አጣን” ብለን አንቆጭም። እናም፣ የቅድመ አያቶች የፈጠራ ውጤቶችን ወይም የስልጣኔ ቅርሶችን ታቅፈን፣ የፈጠራ ባህላቸውንና የስልጣኔ ሰብዕናቸውን በትንሹ ለማወቅ፣ ለማክበርና ለማሳደግ አንዳች ጥረትና ሙከራ ልናደርግ ይቅርና ቅንጣት ፍላጎት ወይም ምኞት እንኳ አይታይብንም። ይባስ ብለን፣ ከስልጣኔ ባህል የተገኙ ቅርሶችን፣ ወደፊት የስልጣኔ ባህል እንዳይፈጠር ለማጨናገፍና ብቅ ካለም በእንጭጩ ለመቅጨት እንጠቀምባቸዋለን። የስልጣኔን ራዕይ ለማውለብለብ፣ የፈጠራ ባህልን ለማነቃቃት፣ የስኬት ፋናን ለመለኮስ አለኝታ ሊሆኑን የሚችሉ የስልጣኔ ዘመን ማስታወሻ ቅርሶችን፣ በተቃራኒው የስልጣኔ ተስፋን ለማጨለም፣ የፈጠራ ጭላንጭልን ለማዳፈንና የስኬት ሰብዕናን ለማኮላሸት የሚያገለግሉ የጥፋት አርማና መሳሪያ እንዲሆኑ አድርገናቸዋል። የስልጣኔ ባህል ምንነትን አለማወቅ፣ ማርከስና ማጥፋት ማለት ይሄ ነው - ከዚህ የባሰ ክፉ ኋላቀርነት ምናለ? የሳር ጎጆ፣ የውሃ እንስራ ወይም ሌላ ቅርስ እንደ “ባህል” ማሳያ ተደርጎ ሲቀርብ፤ ምን አይነት ሃሳቦች እንደሚሰነዘሩ መታዘብ ትችላላችሁ። ከሺ አመታት በፊት እነዚህን ነገሮች የፈለሰፉ ሰዎች ታላቅ የፈጠራ ባህል እንደነበራቸው በማስታወስና በአርአያነታቸው በመነቃቃት፣ እኛም እንደነሱ ከድንዛዜ የሚያላቅቅ የፈጠራ ባህል በመገንባት ሕይወትን ይበልጥ የሚያሻሽሉ ነገሮችን እንፍጠር የሚል መልእክት ያዘለ አስተያየት ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? በተቃራኒው አዲስ የተሻለ ነገር ሳንፈጥር፣ ከሳር ጎጆ እና ከውሃ እንስራ ጋር ተጣብቀን የመቀጠል ቅዱስነት ዘወትር ይሰበካል። በጣይቱ ሆቴል ቃጠሎ ሰበብ ከተለኮሰው ሰሞነኛ ንትርክ የምታገኙት መልእክትም ተመሳሳይ ነው። የጣይቱ ሆቴል ላይ የደረሰው ቃጠሎ እንዲያ አነጋጋሪ የሆነው ለምን እንደሆነ ራሳችሁን ጠይቁ። የህንፃው የሆቴል አገልግሎት ልዩና ድንቅ ስለሆነ አይደለም። ቅርስ ስለሆነ ነው። ነገር ግን በቅርስነት ዋጋ የሚኖረው፣ በፈርቀዳጅነት የተሰራ በመሆኑ፤ የፈርቀዳጅነት ባህልን የምናከብር ከሆነ ብቻ ነው። እንግዲህ ፍረዱ። በቃጠሎው ዙሪያ ሲጧጧፍ በሰነበተው ንትርክ፤ የፈርቀዳጅነት ሰብእናንና ባህልን ስለማክበር ሲነሳ ሰምታችኋል? ዛሬ በዘመናችንም በሆቴል አገልግሎትም ሆነ በሌላ መስክ እጅግ የተሻሉ አዳዲስ ሆቴሎች ወይም ሕንፃዎች ወይም ሌሎች ስራዎች እንዲገነቡ የሚያነሳሳ ቅርስ ነው ሲባል አጋጥሟችኋል? አይመስለኝም።    
እንግዲህ የየአገራችንና የዘመናችን ነገር እንዲህ ነው። እዚህ አገር፣ ጥንታዊ የስልጣኔ ታሪክ ተፈጥሮ እንደነበር እናውቃለን - ትክክለኛ ምንነቱንና ዋነኛ መንስኤዎቹን ግን በደንብ አናውቃቸውም። የስልጣኔው ታሪክ ተዳክሞና ተሸርሽሮ፣ በቦታው ውድቀትና ኋላቀርነት እንደተተካ በተወሰነ ደረጃ ይገባናል - የውደቀቱን ሰበቦችንና የኋላቀርነቱን ምንነት በውል አልተገነዘብናቸውም። አቶ ውብሸትን እና አቶ ዳንኤልን በምስክርነት ላቅርብላችሁ፡፡
የአመት በዓል ዝግጅቱን ስፖንሰር ያደረገው የጊዮርጊስ ቢራ ድርጅትን በማመስገን የጀመሩት አቶ ውብሸት፣ የድርጅቱ ትብብር በርካታ አስርት አመታትን ያስቆጠረ ነው በማለት አድናቆታቸውን ገልፀዋል። የፌሽታ ስሜታቸው የተቀየረው፣ ስለ ኢትዮጵያ ባህል ሲናገሩ ነው። አገሪቱ በኢኮኖሚ እያደገች ቢሆንም በባሕል ግን እየከሰረችና ወደ ታች እየወረደች መሆኗን አቶ ውብሸት ገልፀው፣ የገና በዓል አከባበርን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። የአገራችን ባህል፣ በገና ጨዋታና በጭፈራ፣ ጠላና ድፎ ዳቦ አዘጋጅቶ አብሮ በመብላትና በመጠጣት በዓሉን ማክበር ነው ያሉት አቶ ውብሸት፣ የገና ዛፍ ባዕድ ነው፤ የውጭ ባህል ወረራ ነው በማለት በቁጭት ካወገዙ በኋላ፣ ፈረንጆች በሚያዘወትሩት ትልቅ ሆቴል ካልሆነ በቀር የገና ዛፍ አያስፈልግም ብለዋል። በአገራችን ባህል፣ ለገና በዓል አቅም ያለው ጋን ሙሉ ጠላ ይጠምቃል፤ ሌላው እንደ አቅሙ በእንስራ ይጠምቃል፤ አቅም ያነሰው ደግሞ እንስሪት በምትባል ይጠምቃል በማለትም አብራርተዋል - አቶ ውብሸት። ግን፣ ቢራ ማምረትንና ቢራ መጠጣትን እንደ ባህል ወረራ በስም ጠቅሰው አላወገዙም።
በአቶ ውብሸት አስተሳሰብ ከሄድን፣ ጠላ፣ ድፎ ዳቦ፣ ጋን፣ እንስራና እንስሪት የመሳሰሉ ናቸው የአገራችን ትልልቅ ነገሮች። እነዚህ ከጥንት የወረስናቸውን እቃዎችና ልምዶች ይዘን መቀጠል ነው ትልቁ ቁም ነገር። ምንኛ ተሳስተዋል! የአገራችንን ጥንታዊ ስልጣኔና ባህል ፈፅሞ አናውቀውም ማለት ነው። የያኔዎቹ የስልጣኔ ሰዎች፣ ከአያት ከቅድመ አያት የወረሱትን ነገር ብቻ ይዘው የሚቀጥሉ ሰዎች አልነበሩም። የፈጠራ ሰዎች ነበር።
የመመርመር፣ የመማር፣ የማወቅ ፍላጎት የነበራቸው የአገራችን የስልጣኔ ሰዎች፣ የፈጠራ፣ የሥራና የመሻሻል (የመበልፀግ) ፍቅራቸውም የዚያኑ ያህል ተአምረኛ ነበር። ከዛፍ እየሸመጠጡ የመብላትና ዋሻ ውስጥ የማደር ልምድን ከአባቶቻቸው ስለወረሱ ያንኑን የሙጢኝ ብለው ሕይወታቸውን ከመግፋት ይልቅ፤ አእምሯቸውን ተጠቅመው እውቀትንና ሙያን አዳብረው፣ በበሬ የማረስ ዘዴንና የጎጆ ቤት አሰራርን ፈጥረዋል። ጋንና እንስራን የማበጀት፣ ጠላና ዳቦ የማዘጋጀት ጥበብን ፈልስፈዋል።
የያኔውን የስልጣኔ ባህል የምናፈቅር፣ የያኔዎቹን የስልጣኔ ጀግኖች የምናከብር ከሆነ፣ ያወረሱንን ነገር የሙጢኝ ይዘን መቀመጥ ሳይሆን፣ በአርአያነታቸው ተነቃቅተን፣ የእውቀትና የፈጠራ ባህላቸውን በመከተል ገና ድሮ ድሮ፣ ከሸክላ ቴክኖሎጂ በተጨማሪ የብረትና የፕላስቲክ ቴክኖሎጂ መፈልሰፍ፣ ከጠላና ጠጅ አልፈን የወይን ጠጅና የቢራ ፋብሪካ መፍጠር በቻልን ነበር። ግን አላደረግነውም። የያኔው የስልጣኔ ባህል ተዘንግቶና ጠፍቶ፣ የስልጣኔ ቅርስና ቅሪት ብቻ ነው የተረፈን - እንስራና እንስሪት። ይሄ፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ የውድቀትና የኋላቀርነት አርማ ነው። አሳዛኙ ነገር፤ ይህንን አርማ በማውለብለብ ከውድቀት የምንድን ይመስላቸዋል። የውድቀታችንን ምንነትና ሰበቦችን አልተገነዘብነውም ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው። በእርግጥ ይሄ ጉድለትና ስህተት፣ የአቶ ውብሸት ብቻ አይደለም። የብዙዎቻችን ነው። በዚያ ላይ የፍልስፍና ወይም የታሪክ ምሁር ባለመሆናቸው፤ ነገሩን ቢስቱት ብዙም አይገርምም።         
የአቶ ዳንኤል ስህተትም ተመሳሳይ ነው። የገና ዛፍና ከረሜላ የመሳሰሉ ነገሮች ባዕድ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ከበዓሉ በፊት ለአንድ ወር ያህል የሚዘልቅ የገና ጨዋታ ውድድር እንዲዘጋጅ ሃሳብ ያቀረቡት አቶ ዳንኤል፤ የበዓሉ እለት የፍፃሜ (የሻምፒዮና) ውድድር የሚካሄድበት ቀን መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል። እስቲ አስቡት የገና ጨዋታ ለወር ያህል ሲካሄድ! ማለቴ፣ የጨዋታ ውድድር በተፈጥሮው አዝናኝ መሆን የለበትም እንዴ? ለጨዋታ ያህል፤ ከእንጨት የተሰራችውን ትንሽ ኳስ፣ ከቆልማማ እንጨት በተሰራ ከዘራ የመሰለ እንጨት እየለጉ መሯሯጥ፣ በአመት አንዴ ምንም አይደለም። ከጨዋታ አልፎ የጨዋታ ውድድር ለመሆን ግን፣ ጨዋታው ከ“መሯሯጥ” ያለፈ አዝናኝ ባህርያት ሊኖሩት ይገባል። ከነዚህ ባህርያት መካከል አንዱ፣ የተጫዋችን ብቃት በቀጥታ ለማየትና ለማድነቅ ያስችላል ወይ የሚል ጥያቄ ያመጣል። የገና ጨዋታ ከመለጋትና ከመሯሯጥ ያለፈ ብቃት ለማየት አያመችም። ሁለተኛው የማራኪ ውድድር ባህርይ፣ ለተመልካች ያለው አመቺነት ነው። የገና ጨዋታ ለተመልካች አያመችም - ተጫዋቾችን እየተከተለና እየሮጠ መመልከት አለበት ካልተባለ በቀር። ሦስተኛ የማራኪ ውድድር ባህርይ፣ የሚያረካ ግብ ወይም ልብ የሚሰቅል የግብ ሙከራ ነው። የገና ጨዋታ ግን፣ እየለጉ ከመንጎድ ውጭ በውል የሚታወቅ ሌላ ግብ የለውም። በአጠቃላይ፣ በተለምዶ የሚታወቀው የገና ጨዋታ፣ (በአንዳች የፈጠራ ሃሳብ ካልተሻሻለ በቀር... ማለትም በስልጡን የፈጠራ ባህል አንዳች ለውጥ ካልተደረገበት በቀር) የመዝናኛ ውድድሮችን መመዘኛ አያሟላም። ተወዳጅነትንና ተዘውታሪነትን ያላተረፈው ለምን ሆነና?
አገር አቀፍ የገና ሻምፒዮንሺፕ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ዳንኤል ግን፣ ከዚህም በተጨማሪ፣ በየቤታችን በገና ዛፍ ፋንታ ከዘራ የመሰለችውን እንጨት ተክተን በመብራቶች እናስውባት ብለዋል። ከዘራ የመሰለችውን እንጨት እንዴት እንደምናቆማት እንጃ። የገና ዛፍ፣ ቢያንስ ቢያንስ የልምላሜ ምኞትንና ተስፋን ያመላክታል። በቀለማት ሲደምቅና በመብራቶች ሲንቆጠቆጥ ደግሞ፣ የብሩህነትን መንፈስ ይፈጥራል። ከዘራ የመሰለ እንጨት ግን... ደግሞምኮ፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መብራቶች “የኢትዮጵያ ባህል” አይደሉም። ምን ለማለት ፈልጌ ነው፤ በነበርንበት ቦታ ላይ እየረገጥን ወይም ባለንበት ቦታ ላይ እንደተቀመጥን እንኑር የሚል ሃሳብ፣ የስልጣኔና የፈጠራ ባህልን ሳይሆን የውድቀትና የድንዛዜ ባህልን የሚያበረታታ ሃሳብ ነው። መፍጠርና መሰልጠን ያልቻለ ደግሞ፤ ያው ከኩረጃ ውጭ አማራጭ የለውም። በሌላ አነጋገር፣ የውድቀት መንስኤና ሰበብ የሆኑ ነገሮች ናቸው እንደ መፍትሄና ፈውስ እየተቆጠሩ ያሉት።
እንግዲህ፣ የአገራችን ነገር እንዲህ ከሆነ፣ “ልዩና ድንቅ አገር” የሚያስብላት ነገር ምንድነው? አገሪቱ የድንዛዜ ወይም ቆሞ የመቅረት አስተሳሰቦች እንደነገሱባት የሚመለከት ሰው፣ “ልዩና ድንቅ አገር” መሆኗን ቢጠራጠር አይገርምም። ምናልባት፣ በየአለም ዙሪያ በየአገሩ የሚኖሩ ሰዎች፣ በየፊናቸው የየራሳቸው አገር ብርቅና ድንቅ ሆኖ ስለሚታያቸው ይሆን፣ ኢትዮጵያ ልዩና ድንቅ ናት የምንለው? “ሁሉም የየራሱን ሲያደንቅ እሰማለሁ” ተብሎ እንደተዘፈነው ማለቴ ነው። ግን አይደለም። ለምሳሌ የአውሮፓን የስልጣኔ ባህል የማይወዱ፣ የሚያንቋሽሹና ለማፈራረስ ሌት ተቀን የሚምሱ የአውሮፓና የአሜሪካ ምሁራን ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
እንዲያውም በ20ኛውና በ21ኛው ክፍለ ዘመን የምዕራባዊያንን ስልጣኔ ማንቋሽሽ የአብዛኛው ምሁርና የብዙ አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት ዋና ምልክት እስከ መሆን ደርሷል ማለት ይቻላል። ከእንግሊዝ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣና ቢቢሲን፣ ከአሜሪካ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ፣ ሃፊንግተን ፖስት ድረገፅ፣ እና ሲኤንኤን ቴሌቪዥን... በየአጋጣሚው የአፍሪካን ባህልና አኗኗርን ሲያሞካሹ ተመልከቱ - የአውሮፓንና የአሜሪካን እያጣጣሉ። በቃ፤ እንደ ወግ ይዘውታል። የምሁርነት፣ የፍትሃዊነትና የቅድስና ምልክት ይመስላቸዋል።
አይግረማችሁ። በአዲስ አበባ የሚኖር ደራሲ፣ ዘፋኝ፣ ሙዚቀኛ፣ ወይም ጋዜጠኛ፣ ወደ ቆላማ አካባቢ የሃመር ተወላጆች  ወደሚኖሩበት አካባቢ ሄዶ፣ አኗኗራቸውን ሲያደንቅና ከተሜነትን ሲያንቋሽሽ እንደምንሰማው ማለት ነው። የወገኛ ነገር! እዚያ እጅጉን በአድናቆት ያሞገሰው አካባቢ ውስጥ መኖር አይፈልግም፤ ወደሚያንቋሽሸው የከተማ ኑሮ ለመመለስ ይሮጣል። ለሰው ልጅ ትልቅ አክብሮትና ፍቅር ያለው ሰው፤ የቆላማው አካባቢ የድህነት ኑሮና ኋላቀር አኗኗር እንዲሻሻል ይመኛል እንጂ፤ የተመቻቸውና የደላቸው ይመስል አኗኗራቸውን እያደነቀ፣ “ሳይበረዝና ሳይከለስ” እንዲቀጥል ይፈልጋል? ማለቴ፣ ልብስ አለመልበስ እንዴት እንደ ስልጣኔና እንደ ባህል ይቆጠራል? ባህል ማለትኮ በሰፊው ስር ለመስደድ የበቃ የፈጠራ ውጤትና ስኬት ማለት ነው - ለምሳሌ ልብስ መስራትና መልበስ።
ለማንኛውም፣ ከኛው ወገኞች ባልተናነሰ መልክ፣ የአፍሪካን ወይም የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ እየቆጠሩ ድንቅ ሃተታ የሚያቀርቡ ወገኛ የውጭ ምሁራን ጥቂት አይደሉም። ነገር ግን፣ ከወገኞቹ ተርታ የማይመደቡ ምሁራን መኖራቸውም አይካድም። ታዋቂው የታሪክና የፖለቲካ ምሁር፣ ሳሙኤል ሃቲንግተን የኢትዮጵያ ስልጣኔ ከዓለም ሁሉ የተለየ እንደሆነ የሚናገሩ ቢሆኑም፣ ከወገኞቹ ተርታ አይደሉም። ለማስመሰልና ለወጉ ያህል፣ ወይም ዘረኛ ላለመባል በማሰብ የአፍሪካ ባህልን ለማድነቅ አይሯሯጡም። እንዲያውም፣ “አፍሪካዊ” ሊባል የሚችል ስልጣኔ ወይም የባህል ቅኝት የለም ይላሉ - ሃቲንግተን። እና ለምን ይሆን፣ ኢትዮጵያ ከሌሎቹ ሁሉ ትለያለች በማለት የፃፉት?
Clashes of Civilizations በተሰኘው መፅሃፋቸው ሰፊ የታሪክና የፖለቲካ ትንታኔ ያቀረቡት ሃቲንግተን፣ በአጠቃላይ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ ከጥንት እስከ ዛሬ በታሪክ ተመዝግበዋል ተብለው ብዙ የታሪክ ምሁራን የሚስማሙባቸው የስልጣኔ ቅኝቶች ከ15 እንደማይበልጡ ይገልፃሉ። ከእነዚህ ውስጥ፣ ጥንታዊውን የግብፅ ስልጣኔ ጨምሮ፣ 7ቱ ስልጣኔዎች ዛሬ የሉም። ጠፍተዋል፣ እንደ ግብፅ ፒራሚዶች ቅርስ ብቻ ነው የቀራቸው። እንዴት መሰላችሁ? ዛሬ የአብዛኞቹ ግብፃዊያን አስተሳሰብና እምነት፣ አኗኗርና ቋንቋ ከጥንታዊው የግብፅ ስልጣኔ ጋር ብዙም ግንኙነት የለውም። የጥንታዊ ግብፅ ቋንቋ፣ ከዛሬዎቹ ግብፃዊያን ቋንቋ ይልቅ ለኢትዮጵያዊያን ቋንቋ የቀረበ ነው በሚል አነስተኛ መዝገበ ቃላት የታተመውም በዚሁ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። እንደ ተረት የሚቆጠረው የሜሶፖታሚያ - የባቢሎን ስልጣኔም እንዲሁ፣ ከዛሬዎቹ የኢራቅ ነዋሪዎች ጋር ይህ ነው የሚባል ግንኙነት የለውም፤ የያኔው ስልጣኔ ሞቷል። የሞተው ሞቶ፣ ዛሬ ያሉት መሰረታዊ የባህል ቅኝቶች 7 ወይም 8 እንደሆኑ የሚናገሩት ሃቲንግተን፤ በስም ይዘረዝሯቸዋል - የቻይና ዙሪያ የባህል ቅኝት (እነ ኮሪያንና ቬትናምን ያካተተ)፣ የጃፓን የባህል ቅኝት፣ የራሺያ ዙሪያ የባህል ቅኝት፣ የአውሮፓና የአሜሪካ የባህል ቅኝት፣ የመካከለኛው ምስራቅና የመሰሎቹ የባህል ቅኝት፣ የህንድ ዙሪያ የባህል ቅኝት፣ እንዲሁም የላቲን አሜሪካ የባህል ቅኝት።
እነዚህ ሰባት መሰረታዊ የባህል ቅኝቶችን የዘረዘሩት ሃቲንግተን፣ አብዛኞቹ ምሁራን “አፍሪካዊ” ሊባል የሚችል የባህል ቅኝት እንደሌለ ይስማማሉ በማለት ያክላሉ። ሰሜን አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ቅኝት የሚካተት ነው። ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት፣ እርስ በርስ የሚያስተሳስር የባህል ቅኝት የላቸውም - የጎሳ ስሜት የተንሰራፋባቸው ናቸውና። ምናልባት ወደፊት፣ በደቡብ አፍሪካ አስኳልነት፣ “የአፍሪካ” ሊባል የሚችል የባህል ቅኝት ሊፈጠር እንደሚችል ሃቲንግተን ይገልፃሉ - Throughout Africa tribal identities are pervasive and intense, but ... conceivably sub-Saharan Africa could cohere into a distinct civilization, with South Africa possibly being its core state (ገፅ 47)።
ወደፊት ሊፈጠር ይችላል የተባለለት የአፍሪካ ቅኝትን ጨምሮ፣ በጥቅሉ የዛሬዋን አለማችን በ8 የባህል ቅኝቶች ይከፋፍሏታል - ሃቲንግተን። ኢትዮጵያ ግን ወደፊት በሚፈጠረው የአፍሪካ አገራት ቅኝት የምትመደብ አይደለችም። ከሌሎቹ የባህል ቅኝቶችም ውስጥም እንደማትካተት የሚናገሩት ሃቲንግተን፣ “ከታሪክ አንፃር፣ ኢትዮጵያ ራሷን ችላ የምትጠቀስ የባህል ቅኝት ናት” ብለዋል (Historically, Ethiopia constituted a civilization of its own)።  
ከሞላ ጎደል፣ ሁሉም አገራት በእነዚህ 8 የባህል ቅኝቶች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው - ከሁለት አገራት በስተቀር። ብቸኛ አገራት “Lone Countries” ተብለው በሃቲንግተን ከተፈረጁ አገራት መካከል አንዷ፣ ሃይቲ ናት - ከየትኛውም ቅኝት ያልሆነችና የራሷ ቅጥ የያዘ የባህል ቅኝት የሌላት አገር። ሃቲንግተን በመፅሃፋቸው ገፅ 136 ላይ እንደገለፁት፣ ሁለተኛዋ ብቸኛ አገር፣ ኢትዮጵያ ናት - ራሷን ችላ እንደ ልዩ የባህል ቅኝት የምትቆጠር። ጃፓን እንደ ሦስተኛዋ ብቸኛ አገር እንደምትመደብ በመጥቀስም፣ ራሷን የቻለች የአለማችን አንድ የባህል ቅኝት አድርገዋታል።
ሃቲንግተን ኢትዮጵያ ልዩ አገር መሆኗን የጠቀሱት፣ በባህል ቅኝት አመዳደብ ብቻ አይደለም። በባህል ቅኝቶች መካከል በሚኖር ግንኙነትም፣ ኢትዮጵያ በጣት ከሚቆጠሩ ልዩ አገራት መካከል አንዷ ናት። የዛሬዎቹ የባህል ቅኝቶችም ሆኑ በሰው ልጅ ረዥም የበርካታ ሺሕ ዓመታት ታሪክ ውስጥ የተመዘገቡ 15 ያህል የባህል ቅኝቶች፣ በብዙ መልኩ የሚለያዩ ቢሆኑም ሙሉ ለሙሉ የተነጣጠሉ ናቸው ማለት አይደለም።
የባህል ቅኝቶች፣ በየዘመናቸው እርስበርስ አዎንታዊና አሉታዊ ግንኙነቶችን እንደሚያካሂዱ ሃቲንግተን ገልፀው፤ የንግድ ግንኙነትንና  የድንበር ወረራን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። የግሪኩ እስክንድር፣ እስከ ህንድና ግብፅ፣ እስከ አፍጋኒስታንና ራሺያ ድንበር ድረስ ወረራ የማካሄዱን ያህል፣ የሞንጎል ንጉስም በአለም ታሪክ ወደር የሌለው ሰፊ ወረራ በማካሄድ ሰፊ ግዛት ተቆጣጥሯል። የቱርክ፣ የግብፅ እና የአረብ ገዢዎችም በየአቅጣጫው ዘምተው ገዝተዋል። የመጨረሻው የግዛት ወረራ የተካሄደው በአውሮፓ ገዢዎች እንደሆነ ይታወቃል - አፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር የወደቀችበት ወረራ። በአጠቃላይ ሲታይ፣ ሃቲንግተን እንደሚሉት፣ በአንድ ወይም በሌላ ወቅት፣ በወረራ ወይም በሌላ ምክንያት፣ ቅኝ ያልተገዛ አገር ወይም ያልተንበረከከ የባህል ቅኝት የለም ማለት ይቻላል - ከሶስት አገራት ወይም ከሶስት የባህል ቅኝቶች በስተቀር። ጃፓን፣ ራሺያ እና ኢትዮጵያ ናቸው ሶስቱ አገራትና ሶስቱ የባህል ቅኝቶች። Only Russian, Japanese, and Ethiopian civilizations, all three governed by highly centralized imperial authorities, were able to resist... and maintain meaningful independent existence - ገፅ 51።
እሺ፣ ኢትዮጵያ ብርቅና ድንቅ አገር ናት። ግን፣ ብርቅና ድንቅ አገር ናት የምትሰኝበትን ባህሪዋንና ምንነቷን ከነመንስኤው ማወቅ ያስፈልጋል።      

አቶ አንዳርጋቸው ባለፈው ወር ከባለቤታቸው ጋር በስልክ ተነጋግረዋል

የእንግሊዝ የፓርላማ አባላትን የያዘ የልኡካን ቡድን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከእስር ማስፈታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመደራደር በቀጣዩ ወር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ዘ ኢንዲፔንደንት ትናንት ዘገበ፡፡
ሁሉንም የእንግሊዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባልነት የያዘው የፓርላማ አባላት የሰብዓዊ መብቶች ቡድን ምክትል ሊቀመንበር ጀርሚ ኮርባይን የሚመሩት የልኡካን ቡድኑ፣ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በመምከር የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ እንዳይሆንና ግለሰቡ ከእስር እንዲፈቱ ለማስቻል እንደሚሰሩ ዘገባው አመልክቷል፡፡አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንግሊዛዊ ዜግነት ያላቸው እንደመሆኑ የእንግሊዝ መንግስት ጉዳዩን አጽንኦት ሰጥቶ መከታተልና ግለሰቡን ከሞት ማዳን ይጠበቅበታል ያሉት ኮርባይን፤ ቡድኑ አቶ አንዳርጋቸው ግልጽ ባልሆነና ተቀባይነት በሌለው የህግ አካሄድ ለእስር ተዳርገዋል ብሎ እንደሚያምን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ አቶ እንዳርጋቸው የአሸባሪ ቡድን አባል ቢሆኑም በእስር ላይ ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ነሃሴና ታህሳስ ወር ላይ ከተደረጉት ሁለት የመንግስት ተወካዮች ጉብኝቶች ውጭ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለመጎብኘት እንዳንችል አግዶናል ብለዋል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ገልጸው፣ በግለሰቡ ላይ የተጣለው የሞት ፍርድ ተፈጻሚ እንዳይሆን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ማድረጉን እንደቀጠለበትም አስረድተዋል፡፡በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የኢትዮጵያን መንግስት ለማፍረስ የሚሰራ አሸባሪ ቡድን አባል ናቸው፣ በእስር ላይ ሆነውም ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው፤ እስረኞችን ማሰቃየት ኢሰብአዊ ድርጊት እንደመሆኑ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ  አይደለም ሲሉ መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ግን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ከቅርብ አመታት ወዲህ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚፈጸምባቸው ስቃይ እያየለ መምጣቱን የሚያመላክት መሆኑን አክሎ ገልጿል፡፡አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ባለፈው ወር እንግሊዝ አገር ወደምትገኘው ባለቤታቸው ስልክ ደውለው መገናኘታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአብዛኛው ስለልጆቻቸው ጉዳይ እንዳወሩ፣ ደህንነታቸውን እንደገለጹላቸው፣ እንዲሁም ለልጆቼ የማይሆን ተስፋ መስጠት አልፈልግም ማለታቸውን ባለቤታቸው እንደተናገሩ አመልክቷል፡፡



Published in ዜና

ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለጉዳቱ መባባስ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያን ተጠያቂ አድርገዋል
“ቃጠሎው ከጃዝ አምባ አልተነሳም” የጃዝ አምባ ዋና ሥራ አስኪያጅ
እሣቱ ከጣይቱ ኪችን አለመነሳቱን አረጋግጣለሁ - አቶ አያሌው ታደሰ የጣይቱ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ
አጋጣሚው ምትክ የማላገኝላቸውን ነገሮች ያጣሁበት ክፉ አጋጣሚ ነው - የፊልም ፕሮዳክሽን ባለቤት

ባለፈው እሁድ ማለዳ ላይ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ታሪካዊው የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል እሣት መነሻ እያወዛገበ ነው፡፡ ፖሊስ እሳቱ የተነሳው በጃዝ አምባ አዳራሽ ውስጥ በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመሮች መጠላለፍ ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ ቢገለፅም እሳቱ ከጃዝ አምባ አለመነሳቱን የጃዝ አምባ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርምያስ ፋንቱ ገልፀዋል፡፡የጃዝ አምባ የኤሌክትሪክ ሲስተም አዲስና ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ለእንዲህ አይነት አደጋ የሚጋለጥበት ምንም ምክንያት እንደሌለና ላለፉት አራት ዓመታት ምንም ዓይነት ችግር አጋጥሞ እንደማያውቅ የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ፤ ፖሊስ እሳቱ የተነሳው ከጃዝ አምባ ነው ማለቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ “ከሙዚቃ መሳሪያ ጋር በተገናኘ እሳቱ ተነስቷል እንዳይባል እንኳን እሁድ ጠዋት የጃዝ አምባ ሰራተኛ የሆነው ልጅ ገብቶ መድረኩን ለቴአትር ዝግጁ ለማድረግ ሁሉንም የሙዚቃ መሳሪያ አነሳስቶ ነበር” ብለዋል፡፡ ሌላው እሳቱ ከጃዝ አምባ እንዳልተነሳ እርግጠኛ የሆኑበትን ምክንያት አቶ ኤርሚያስ ሲናገሩ፤ የህብረት ባንክና የጃዝ አምባ ሲስተም አንድ መሆኑን ጠቁመው፣ እሳቱ ተነስቶ ከጀርባ በኩል ጭስ ሲታይ ሰዎች ከኤቲኤም ማሽን ብር እያወጡ እንደነበር አስታውሰው፣ እሳቱ ከጃዝ አምባ ቢነሳ ኖሮ ኤቲኤም ማሽኑ አይሰራም ነበር  ሲሉ እሳቱ ከጃዝ አምባ ተነሳ መባሉን እንደማይቀበሉት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም በታዋቂዎቹ ሙዚቀኞች አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ሄኖክ ተመስገን፣ ግሩም መዝሙር፣ ዮናስ ጎርፌና ሳሙኤል ገዛኸኝ የተቋቋመው ጃዝ አምባ፤ በቃጠሎው ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ውድመት ደርሶብኛል ብሏል፡፡ የጃዝ አምባው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ፋንቱ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በአደጋው የተለያዩ እጅግ ውድ ዋጋ የሚያወጡ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎቻቸው ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልፀው እሳቱ ገና በጀመረባቸው ደቂቃዎች ጉዳዩን ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ብናሳውቅም አፋጣኝ ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም ብለዋል፡፡ “እሳት አደጋዎች ዘግይተው መድረሳቸው ሳያንስ ከስፍራው ከደረሱም በኋላም አደጋውን ለመከላከል ያሳዩት ቸልተኝነት ጉዳቱ እንዲባባስ አድርጎታል ብለዋል፡፡
እነመርሃዊ ስጦታ፣ ጋሽ ባህታ፣ ግርማ ነጋሽና መሰል አንጋፋ የሙዚቃ ሰዎች ወደ ሙዚቃ እንዲመለሱና ሞራላቸው እንዲጠገን በማድረጉ በኩል ጃዝ አምባ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ፤ ቃጠሎው በእነዚህ ሰዎችም ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጃዝ አምባውን ወደ ቀድሞው ሥራው ለመመለስ በኮንሰርትም ሆነ በሌላ መንገድ ገቢ ለማሰባሰብ ቃል መገባቱንና ብዙ ተዘግቶ ይቆያል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡ የአዲስ ተስፋ ኮሙኒኬሽንና ኢንተርቴይመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስ ተስፋ በበኩላቸው፤ በቃጠሎው ምትክ የሚያገኙላቸውን ውድ ነገሮች ማጣታቸውን ጠቁመው፣ “ይህ በህይወቴ ብዙ ነገሬን ያጣሁበት ክፉ አጋጣሚ ነው” ብለዋል፡፡ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ሞት ጊዜ አርቲስቶች የሰሩትን ስራ በኃላፊነት ተረክበው ሲሰሩ እንደነበር የተናገሩት አቶ አዲስ፤ ሥራው ያለ ቀሪ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ገልፀዋል፡፡ በቀርቡ ሠርተው ያጠናቀቁት “በቅኝትሽ” የተሰኘ አዲስ ፊልምን ጨምሮ የሠርግ ስነስርዓታቸውን ሲፈፅሙ የተቀረፁ የቪዲዮና የፎቶግራፍ ቅጂም ያለምንም ምትክ ወድሞብኛል ብለዋል፡፡ በገንዘብ ልተካቸው የማልችላቸው በርካታ ዘጋቢ ፊልሞችና ምትክ የማላገኝላቸው ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ወድመውብኛል ሲሉም ሁኔታውን በሃዘን ገልፀዋል፡የእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ፤ በቃጠሎው ወቅት በፍጥነት ከቦታው አለመድረሳቸውንና ከደረሱም በኋላ እሣቱን ለማጥፋት ቸልተኝነት ማሣየታቸውን አስመልክቶ የቀረበባቸውን ቅሬታ፤ የሥራውን ባህርይ ካላማወቅና ከግንዛቤ ማነስ የተሰጠ አስተያየት ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
የእሣት አደጋው ጥሪ በተደረገልን በሁለት ደቂቃ ውስጥ ከሥፍራው ደርሰናል ያሉት ኦፊሰሩ፤ የሆቴሉ እድሜ፣ ርዝማኔና የተሠራበት ቁሳቁስ በፍጥነት ተቀጣጣይ መሆን አደጋውን አባብሶታል ብለዋል፡፡
ሠራተኞቹ ከሥፍራው እንደደረሱ ምንም አይነት ቸልተኝነት አላሣዩም ያሉት አቶ ንጋቱ፤ እሣት እንደ ሻማ እፍ ተብሎ የማይጠፋ በመሆኑና ህዝብ የማይረዳቸው ብዙ ቴክኒካል ነገሮች በመኖራቸው እነሱ እስከሚስተካከሉ ድረስ ደቂቃዎች ማለፋቸው አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡  

Published in ዜና

በኢትዮጵያ ኢስላማዊ መንግስት ለማቋቋም በተለያዩ የሽብር ድርጊቶች ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ የተባሉ ሶስት የውጭ ሃገር ዜጎች በእስራት ተቀጡ፡፡
“ጀንከታ ሙስሊም” የተሰኘ የጅሃድ አሸባሪ ቡድን በህቡዕ በማቋቋም፣ ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉት የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው አሊ ሂድሮክና መሃመድ ሸሪፍ እንዲሁም የሶማሊያ ዜግነት ያለው አህመድ መሃመድ ሲሆኑ ግለሰቦቹ አባላት በመመልመል፣ በማደራጀትና ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት በኢትዮጵያ ኢስላማዊ መንግስት እንመሰርታለን በሚል ለሽብር ተልዕኮ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡ ሶስቱም ግለሰቦች በዋና ወንጀል ፈፃሚነት የሽብር ድርጊት ለመፈፀም በማቀድ፣ በማሴር፣ በማነሳሳትና ሙከራ በማድረግ በሽብር ተካፋይ ክስ የመሰረተባቸው አቃቤ ህግ በክርክር ሂደቱ አራት ምስክሮችን አቅርቦ ጥፋተኝነታቸውን በበቂ ማስረጃ በማስረዳቱ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወ/ችሎት ግለሰቦቹ ከ4 ዓመት ከ6 ወር እስከ 4 ዓመት ከ8 ወር በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ከትናንት በስቲያ ወስኗል፡፡
በመዝገቡ 1ኛ ተከሳሽ የሆነው አሊ ሃድሮክ በ4 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ  ሲወሰንበት መሃመድ ሸሪፍና አህመድ መሃመድ እያንዳንዳቸው በ4 ዓመት ከ8 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ፍ/ቤቱ ወስኗል፡፡

Published in ዜና

ያጨሰ 1 ሺህ ብር፣ ያስጨሰ 3 ሺህ ብር ይቀጣል

የመቐለ ከተማ አስተዳደር በመዝናኛ ስፍራዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎችና በመሳሰሉት ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ የሚከለክል ህግ ተግባራዊ ማድረጉ ተገለፀ፡፡በመዝናኛ ስፍራዎች ሲጋራ ሲያጨሱ የተገኙ ግለሰቦች ከ1 ሺህ ብር በላይ፣ ሲጋራ እንዲጨስ የፈቀዱ የመዝናኛ ስፍራዎች ባለቤቶች ደግሞ ከ3ሺህ ብር በላይ ቅጣት እንደሚጣልባቸው የጠቆመው የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ሊደረግ የታቀደውን ይህን ህግ በስራ ላይ በማዋል መቐለ የመጀመሪያዋ ከተማ መሆኗንም አስታውቋል፡፡ህጉ ከዚህ በተጨማሪም በስታዲየሞችና ሃይማኖታዊ ዝግጅቶች በሚከናወኑባቸው ስፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ እንደሚከለክል ታውቋል፡፡በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አንድ አስረኛ ያህሉ የሲጋራ ሱስ ተጠቂ እንደሆኑ የአለም የጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል፡፡የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ የሚከለክልና በሲጋራ ሽያጭ ላይ ገደብ የሚጥል  አዋጅ ማጽደቁ ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

ከግል ባለሃብቶች ጋር በሽርክና የሚያካሂደው የቤት ግንባታ ሞዴል ደንብ እየተዘጋጀ ነው

መንግስት በሪል እስቴት ቤቶች ልማት ዘርፍ ከግል ባለሃብቶች ጋር በሽርክና ሊሰማራ ሲሆን ለዚሁ ስራ የሚያገለግል ሞዴል ደንብ እየተዘጋጀ ነው፡፡ የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የአምስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው፣ በመንግስትና በግል ባለሃብቶች ሽርክና ለሚካሄደው የቤት ልማት ሞዴል ደንብ የማዘጋጀት ስራ በግማሽ ተጠናቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቤት ልማት አማራጩን ለማስፋትና የቤት ልማት ዘርፍና አስተዳደር ህግና ስርዓትን የተከተለ እንዲሆን ለማድረግ የሪል እስቴት ልማትና ግብይት የሚመራበት አዋጅ ለማዘጋጀት ታቅዷል፡፡ ለአዋጁ ግብአት የሚሆኑ መረጃዎችን የመሰብሰብና መተንተን ስራ የተከናወነ ሲሆን የአዋጁ ረቂቅ ሰነድ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በመንግስት ቤቶች ልማት በአዲስ አበባ ግንባታቸው የተጀመረ በ20/80 የቤቶች ፕሮግራም 120ሺ 712 ቤቶች፣ ቁጠባን መሰረት ባደረጉ የ10/90 ቤቶች ፕሮግራም 24ሺ258 ቤቶች እንዲሁም በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም 14ሺ213 ቤቶች በድምሩ 159ሺ213 ቤቶች ግንባታቸው እየተካሄደ መሆኑን የጠቆመው የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሪፖርት፤ የተወሰኑት ቤቶች እጣ በመጪው የካቲትና ሚያዝያ እንደሚወጣም አመልክቷል፡፡

Published in ዜና

በሲሚንቶ ገበያ የታየው ለውጥ በቢራ እየተደገመ ነው

   ከነባር የሲማንቶ አምራቾች ላይ ግዙፉ የደርባ ሚድሮክ ፋብሪካ ከዚያም የድሬዳዋው ናሽናል ሲሚንቶ ሲታከልበት እንደታየው በቢራ አምራቾች የተጧጧፈ ውድድርም በአጭር ጊዜ አስደናቂ የዋጋና የአቅርቦት ልዩነት እየታየ ነው፡፡ የዋጋ ንረት በተለመደበት አገር ደንበኞችን የመማረክ ብርቱ ፉክክርና ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ከመታየቱም በተጨማሪ፤ ዘንድሮ ውድድሩን የሚያጠናክሩ አዳዲስ ግዙፍ ፋብሪካዎች ስራ የሚጀምሩበት ዓመት ሆኗል፡፡
ሰሞኑን ሄኒከን ካስመረቀው ፋብሪካ ብዙም ሳይቆይ፣ በጥቂት ሳምንታትና ወራት ሃበሻ ቢራና  ሌላ ግዙፍ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡
በቢዝነስ ውስጥ የመንግስት ድርሻና ጣልቃ ገብነት በቀነሰ ቁጥር፣ የምርቶች ዋጋና የአገልግሎት ጥራት እንደሚሻሻል እንደ ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን የመሳሰሉ ምሁራን በበርካታ አመታት ጥናትና ምርምር ያረጋገጡ ቢሆንም የነፃ ገበያ ውድድር ትሩፋት ያለጥናትና ምርምር በገሃድ ከታየባቸው መስኮች አንዱ የሲሚንቶ ገበያ ነው፡፡ አነስተኛ የግንባታ ስራ የጀመሩ ዜጐች በሲሚንቶ የዋጋ ውድነት፣ ትልልቅ ፕሮጀክት የጀመሩ ኢንቨስተሮች ደግሞ ለባለ አስር ፎቅ ህንፃ የሚበቃ ሲሚንቶ ሲጠይቁ የአንድ ፎቅ ብቻ እየተፈቀላቸው፣ ለዚያውም ተራ እስኪደርሳቸው ግማሽ አመት እየዘገየ፣ የዋጋው ውድነት ታክሎበት ለዓመታት ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ አነስተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ ኢንቨስትመንቶችና የነባሮቹ የማስፋፊያ ውጥኖች ላይ ግዙፉ የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ማምረት ሲጀምር ግን የቀድሞው የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት ተረት ሆነ፡፡ የሲሚንቶ ዋጋ በግማሽ ቀነሰ፡፡ የድሬዳዋው ናሽናል ሲሚንቶ መጠናቀቁና ወደፊትም የናይጄሪያው ናሽናል ሲሚንቶ መጠናቀቁና ወደፊትም የናይጄሪያው ባለሃብት ፕሮጀክት እየተስፋፋ መሆኑ ደግሞ፤ የሲሚንቶ ችግር በነፃ የገበያ ውድድር ለዘለቄታው እንደሚቀየር ይጠቁማል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ መንግስት ከቢራ ቢዝነስ እየወጣ በመጣ ቁጥር፣ የምርትና የአገልግሎት ማሻሻያዎች  እየታዩ መምጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን የነፃ ገበያ ፉክክሩና ትሩፋቶቹ ጐልተው የታዩት ከአዲስ አመት መግቢያ ጀምሮ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሄኒከን፤ ዋልያ ቢራ ምርቱን በ10 ብር ሲያቀርብ ነው፤ አይቀሬው የነፃ ገበያ ትሩፋት በራሱ ጊዜ መዛመት የቀጠለው፡፡ ሌሎቹም ግንባታው እያጠናቀቁ ነው - ለዚያውም በየፊናቸው ሪኮርድ የሚሰብሩ ግዙፍ ፋብሪካዎችን፡፡ እዚህም ጋ ኒያላ፣ ዘመን የመሳሰሉ ምርቶችን ከማስተዋወቅ ጋር፣ ደንበኞችን ለመማረክ የዋጋ፣ የአገልግሎት ፉክክር አጧጥፈዋል፡፡ ቢጂአይ  በ11 ብር የሚሸጠውን አንድ ጃንቦ ብርጭቆ ድራፍት “ሃፒ ሃወር” በማለት ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ በ8 ብር መሸጥ ጀመረ፡፡ ዲያጆ በፊናው፤ በዘጠኝ ብር ይሸጥ የነበረውን አንድ ጃንቦ ሜታ ድራፍት በ8 ብር እንደሚሸጥ ካስታወቀ በኋላ፤ በቅርቡ “ዘመን” በማለት የሰየመውን የቢራ ምርት በ10 ብር መሸጥ ጀምሯል፡፡ ቢጂአይ በበኩሉ፤ ከሰሞኑ  ሁለት ጠርሙስ ጊዮርጊስ ቢራ ለሚጠጣ ደንበኛ አንድ ጠርሙስ መመረቅ ጀምሯል፡ ደንበኞችን ለመማረክ የሚደረገው የዋና የአገልግሎት ፉክክር በዚህ አይቆምም፡፡ በቅርቡ ወደ ገበያ ለመግባት የተቃረቡ አዳዲስ ቢራ ፋብሪካዎች ከደጃችን እየደረሱ ነው፡፡ ሃበሻ ቢራ በቅርብ ሳምንታት ወደ ገበያ እንደሚገባ የገለፀ ሲሆን፣ ዳሽን ቢራ በደብረ ብርሃን የማስፋፊያ ግንባታውን አጠናቆ በመጋቢት ወር በቀን 3 ሚሊዮን ጠርሙስ ቢራ የሚያመርት ግዙፍ ፋብሪካ ያስመርቃል፡፡ ራያ ቢራም ግንባታውን ጨርሶ ወደ ገበያ ለመግባት እየተንደረደረ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ አዳዲስ ቢራ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ሲያስገቡ ፉክክሩ ይበልጥ እንደሚጦፍ መገመት ይቻላል፡፡ የሄኒከን እና የዳሽን ቢራን ዘገባ በገጽ 11 መልከቱ፡፡

Published in ዜና
Page 11 of 18