አንዳንድ ዕውነተኛ ታሪክ ሲቆይ ተረት ይመስላል፡፡ የሚከተለው ትርክት እንዲያ ያለ ጠባይ አለው:-
ሰውየው እሥረኛ ነበሩ አሉ፡፡ በጥንት ዘመን፡፡ ዚቀኛ ናቸው - ነገር አዋቂ፡፡
እሥረኞች “የሻማ” የሚሉት ፈሊጥ አላቸው፡፡ የኢኮኖሚ እርዳታ ነው አንዱ፡፡ የመዝናኛ ጥያቄ ነው ሁለተኛው፡፡
ጠያቂው እሥረኛ - በምን ታሠሩ? አላቸው፡፡
አዲሱ እሥረኛ - አለቃዬ ጠፍቶ
ጠያቂው እሥረኛ - ለምን ጠፋ?
አዲሱ እሥረኛ - ለሠራዊት የመጣ የዩኒፎርም ጨርቅ ወደ መርካቶ አሻግሮ
ጠያቂው እሥረኛ - ታዲያ እርሶ ምን አገባዎት?
አዲሱ እሥረኛ - እሱ እስኪመጣ እዚህ ተቀመጥ ተብዬ ነው
ጠያቂው እሥረኛ - እሺ አሁን እርሶ ምንድነዎት ታዲያ ?
አዲሱ እሥረኛ - ቀብድ ነኛ!
ሁሉንም አሳቋቸው፡፡
እሥረኛው ዋሉ አደሩና ለምርመራ ተጠሩ፡፡
ሄደው ሲመለሱ ፊታቸው ቀልቷል፡፡ ንዴትና እልህ እየተናነቃቸው ነው! የሚቀርባቸው እሥረኛ ጠጋ ብሎ አነጋገራቸው፡፡
“ምነው ከፍቶዎታል?” አላቸው
“መርማሪው አበሳጨኝ!”
“ለምን?”
“ቀበሌህን ተናገር አለኝ - አላውቅም አልኩት”
“ምን ነካዎት አድራሻ መደበቅማ አይቻልም፡፡ መናገር ነበረብዎት!”
“እኔ እምቢ አልኩት - ስለማላምንበትም ነው፡፡ ጣጣው ብዙ ነው”
“እንዴት ነው የማያምኑበት”
“ቆይ ላጫውትህ… አንድ ልጅ ቄስ ት/ቤት ይማራል አሉ፡፡ አንድ ቀን ተገርፎ ወደቤቱ እያለቀሰ ይመጣል፡፡
እናቱ - “ምን ሆንክ ልጄ” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡
ልጁም እየተነፋረቀ፤ “እኚህ የኔታ መቱኝ” ይላታል፡፡
“ምን አድርገሃቸው መቱህ?”
“ሀ በል ሲሉኝ ጊዜ እምቢ አልኳቸው”
“አንተ የሞትክ! ሀ ማለት አቅቶህ ትገረፋለህ?”
“አይ እማዬ የኔታን አታውቂያቸውም፡፡የየኔታ ጉዳቸው መች ያልቃል? - ሀ ስትይ ሁ በይ ይሉሻል። ሁ ስትይ ሂ በይ ይሉሻል…እንዲህ እያሉ እስከ “ፐ” ያለፉሻል!...”
*    *    *
ጣጣው የማያልቅ ችግር ለትውልድ ይተርፋል፡፡ በትምህርት ከሀ እስከ ፐ መጓዝ የማይናቅ መሆኑ ባይካድም፤ ውጣ - ውረዱ፣ መከራው ሰቆቃው አይጣል ነው፡፡ ችግርን ከምንጩ መንቀል ብልህነት ነው። ከፊደልም ከህይወትም መማር ሙሉ ያደርገናል፡፡ ለለውጥ ዝግጁ የምንሆነው አንድም ዕውቀታችን ወደ ጥበብ ሲበስል፤ አንድም ለአዲስ ነገር አዕምሮአችን ክፍት ሲሆን፤እንዲሁም ከስህተታችን ለመማር እንችል ዘንድ ግትርነትን ስናስወግድ ነው፡፡
በሀገራችን የታሪክ ሂደት፤ ትግል፣ ድርድር፣ ዕርቅና ስምምነት፣ ጠቅልሎ ገብቶ ከመንግሥት ጋር መሥራት፣ መጣላትና መክዳት አዘውትረው የታዩ ክስተቶች ናቸው፡፡
በተለይ መከዳዳት እጅግ ተደጋግሞ የታየ ነው፡፡
“ወዳጅን አንዴ መክዳት ይቻላል ሁለት ጊዜ ግን አይቻልም” ceasy to rat but not to re – rat) ይላሉ ዊንስተን ቸርችል፡፡ ትግል ሲከር፣ ዘመን ሲከዳ፣ አቋም ሲሟሽሽ፣ ተስፋ ሲጠፋ፣ በተለይም ወኔ ሲከዳ፤ አሊያም አቋም ሲለወጥ፤ እናት - ክፍልን ትቶ ወደሌላ ሠፈር ይገባል፡፡
መደራደር፣ ዕርቅና መስማማት ከጦርነት እኩል ሜዳ ላይ ናቸው ይባላል፡፡ ጂኬ ቴስተርተን እንደሚለን “መደራደርና መስማማት ማለት ግማሽ ዳቦ ማግኘት ከምንም ይሻላል ነበር፡፡ አሁን ግን በዘመናዊ መንግሥታት ዘንድ ግማሽ ዳቦ ከሙሉ ዳቦ ይሻላል በሚል ተለውጧል”፡፡ ተደራድሮ አንድ ነገር ማግኘት ታላቅ ነገር ነው፡፡ ሆኖም መደራደርን እጅ ከመስጠትና ከክዳት ለይቶ ማየት ያሻል፡፡ ከማጐብደድ መለየት የስፈልጋል፡፡
ደራሲና ፀሐፌ - ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን “በምኒልክ” ተውኔቱ ያለውን አለመርሳት ደግ ነው። “ሸዋም ያው ያባት ልምዱን፣ የባህል ግብሩን፣ በጐበና ሹመት ላይ አጉተመተመ፡፡ አጉረመረመ፡፡ ያኑ የሆድ ክፋት ቅርሱን፣ ምሱን፣ የምቀኛ ተውሳኩን፣ ውስጥ ውስጡን አቀረሸ፡፡ “ማናቸውን ንጉሥ እንበል?!” እያለ፤ ይሄ አዲሱ ጐበና፣ የልቼው ሳይሆን፣ ራሱን እንደንጉሥ ላስጠራ ባይ ተቆናኝ ሆኗል፤ መሾሙንስ ምኒልክ ሾመው፣ መሻሩንስ ማን ይሽርለት ይሆን? እያለ…”
ወገን ሳይኖር፣ አጋር ሳይኖር፣ በዙሪያ ደግ - አሳቢ ሳይኖር፤ ሹመት የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው! በእርግጥ አያሌ ከእናት ፓርቲያቸው የተለያዩ የጥንት የጧት ሰዎች እናውቃለን፡፡ ምናልባትም እነሱም የራሳቸው ምክንያት ይኖራቸው ይሆናል፡፡ ለአንድ የእንግሊዝ ፓርላማ ቀዳማዊት ኤልሣቤጥ አደረጉት የሚባል ንግግር ላይ “እንደኔ ከሆነ፤ ለምን መኖርን መውደድ እንዳለብኝ ወይም ለምን መሞትን መፍራት እንዳለብኝ አንዳችም ምክንያት የለኝም፡፡ የዚህችን ዐለም በቂ ልምድ አግኝቻለሁ፡፡ ዜጋ መሆንም፤ መሪ መሆንም ምን ማለት እንደሆነ አውቄያለሁ፡፡ መጥፎም ጥሩም ጐረቤት ኖሮኝ ያውቃል፡፡ ስለዚህ በራሴ ዕምነት መክዳት ጥሩ እንደሆን ተገንዝቤአለሁ፤ ብለዋል፡፡ ደግና ክፉ መለየት ያለበት ራሱ ባለቤቱ ነው።
የዱሮም ይሁን የአሁን ወዳጅ፣ ከጊዜ በኋላ፤ አቋም ለውጠው ሲገናኙ እንዴት እንደሚገናኙ፣  እንዴት እንደሚወያዩ፤ ግራ ሊገባቸው ይችላል፡፡ ሆድ ለሆድ ተግባብተው? ተቂያቂመው? ወይስ ይቅር ለእግዚሃር ተባብለው፤ ስለአገር ጉዳይ ተስማምተን እንሥራ ተባብለው?
በየትኛውም የሹመት ደረጃ ብንሆን፤ አገርን የሚጐዳ ከሆነ ሥልጣን በቃኝ ማለት መክዳት አይደለም የእንግሊዝ ተወላጁ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዴ ሀይለኛ ግምገማ ተደርጐ አይምሬ የሆነ ግልጽ ሂስ ሲካሄድባቸው፤ “እኔምኮ ዶሮ እስኪጮህ ነበር የምጠብቀው ሥልጣኔን ለመልቀቅ” አሉ፤ አሉ፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንን፤ ተዋግተንም እናምጣው፣ በሰላማዊ ድርድር፤ አሊያም ደጅ ጠንተን፤ ዳገት ቁልቁለት የሌለበት፣ በወርቅ አልጋ፣ በእርግብ ላባ ላይ መተኛት ነው ብሎ ማሰብ፤ ቢያንስ የዋኅነት ነው። “ሳያሽ የጐረሠ ዝንጀሮ በሳል ይመታል” ማለት ይሄው ነው፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

            በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የቆየው 3ኛው የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ ወደ ሩብ ፍፃሜ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ በጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ ዛሬ ናይጀሪያ ከሞሮኮ ፤ ማሊ ከዚምባቡዌ እንዲሁም ነገ ጋቦን ከሊቢያ፤ ጋና ከዲሞክትራቲክ ኮንጎ ይጫወታሉ፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በዘንድሮው የቻን ውድድር ለሚሳተፉ ብሄራዊ ቡድኖች በየደረጃው የሚከፋፈል 3.6 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል፡፡ ከሩብ ፍፃሜው በፊት ይሄው የሽልማት ገንዘብ ይፋ የሆነው ለሻምፒዮናነት ጠንካራ ፉክክር እንዲደረግ ታስቦ እንደሆነ የገለፀው ካፍ ሻምፒዮኑ ብሄራዊ ቡድን 750ሺ ዶላር ከዋንጫው ሽልማት ጋር እንደሚያገኝ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ቻን ተብሎ በሚጠራው አህጉራዊ ሻምፒዮና ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈው የዋልያዎቹ ስብስብ ለትንሳዔው በታዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች መስራት እንደሚያስፈልግ እየተገለፀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሶስት ከሊቢያ፤ ኮንጎ ብራዛቪልና ጋና ጋር ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ተሸንፎ፤ አንድም ጎል ሳያገባ 5 የግብ እዳ አስመዝግቦ በመጀመሪያው ዙር በመሰናበት ከትናንት በስቲያ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡ ዋልያዎቹ በቻን ተሳትፏቸው ደካማ አቋም ማሳየታቸው የብሄራዊ ቡድኑን የወደፊት ጉዞ መነጋገርያ አድርጎታል፡፡
በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጆሃንስበርግ ኦሊቨር ታምቦ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ብሄራዊ ቡድኑ ለቻን ውድድር ሲገባ ጥሩ አቀባበል አድርገውለት ነበር፡፡ ከውድድሩ በምድብ ማጣርያው ሲሰናበት ግን ምንም አይነት ሽኝት አላደረጉለትም፡፡  ቡድኑ ከቻን ተሰናብቶ ባለፈው ሐሙስ ከምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል አዲስ አበባ ሲደርስም የፌዴሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች ካደረጉት ቀዝቃዛ አቀባበል በቀር የተለየ ነገር አለገጠመውም፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ስደተኞች እና መላው ኢትዮጵያውያንም ሆነ እዚህ አገር ቤት ያሉ ወገኖች መላው በቻን የነበረው ደካማ ተሳትፎ የወደፊቱን የእግር ኳስ እድገት እንዳያጨልም ሰግተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በርሆቦት ፕሮሞሽን አስተባባሪነት  የጉዟቸው  ሙሉ ወጭ ተሸፍኖ የቻን ውድድርን ለመዘገብ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀኑት ጋዜጠኞች በደሌ ስፔሻል በፈጠረላቸው እድል መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ በደሌ ስፔሻል ከ600ሺ ብር በላይ ወጭ  አድርጎ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ  ያደረገላቸው የስፖርት ጋዜጠኞች ከአዲስ አድማስ፤ ከሪፖርተር፤ ከኢንተር ስፖርት ፤ ከሊግ ስፖርት እንዲሁም ከኢትዮ ፉትቦል ድረገፅ  የተወከሉ ናቸው፡፡  
በአህጉራዊ ውድድሩ በቀጥታ መረጃ የሚያገኙበትን እድል በመፍጠር፤ ከውድድሩ በተያያዘ የተለያዩ ልምዶችን እንዲቀስሙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እና የሙያ ብቃታቸውን እንዲያዳብሩ በማገዝ ኩባንያው ላደረገው ድጋፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ምስጋናቸውን ገልፀዋል።  የስፖርት ጋዜጠኞቹ፤ በደቡብ አፍሪካ ሁለት ከተሞች ጆሃንስበርግና ብሎምፎንቴን ለ8 ቀናት ቆይታ ነበራቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ብሎምፎንቴን በሚገኘው ፍሪስቴት ስታድዬም በምድቡ  ከኮንጎ እና ከጋና ብሄራዊ ቡድን ያደረጋቸውን ጨዋታዎች 900 ኪሎሜትር የደርሶ መልስ ጉዞ በማድረግ በቀጥታ ተከታትለዋል፡፡ በጆሃንስበርግ ከተማ ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር በመገናኘት በእግር ኳሱ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ምክክር አድርገዋል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ስታድዬሞችን በመመልከትና ታዋቂ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራን ጐብኝተዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የዋልያዎቹ ደጋፊዎች ምን ይላሉ? ፌደሬሽኑስ?
ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ በቻን የምድብ 3 መክፈቻ ጨዋታው ብሄራዊ ቡድኑ በሊቢያ  2ለ0 ከተሸነፈ በኋላ ደስተኞች አልነበሩም፡፡ በቀሪዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ከተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ወደ ብሎምፎንቴን በመምጣት ድጋፍ ለመስጠት የተቸገሩትም የቡድኑ ብቃት ያልጠበቁት ሆኖባቸው ነው፡፡ በዋልያዎቹ የምድብ 3 መክፈቻ ጨዋታ በፍሪስቴት ስታድዬም የተገኙ ኢትዮጵያውያን በስምንት አውቶብሶች ተጉዘው ብሎምፎንቴን የገቡ ነበሩ፡፡ እስከ ስምንት ሺ ይደርሳሉ፡፡ ከኮንጎ በተደረገው ሁለተኛ ጨዋታ ግን ይህ ሁኔታ ተቀዛቀዘ፡፡ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩበት ጆሀንስበርግና ሌሎች ከተሞች ብሎምፎንቴን የመጡት በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከጋና ጋር በተደረገው የምድቡ መጨረሻ ጨዋታ ደግሞ ቡድኑን ለመደገፍ ፍሪስቴት ስታድዬም የተገኙት በከተማዋ የሚኖሩት ሲሆኑ ከሌሎች ግዛቶች የመጡት በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡  
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቻን ውድድር በምድብ ማጣርያው ከተሰናበተ በኋላ በተለያዩ በደቡብ አፍሪካ እየሰሩ  የሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን በዋልያዎቹ አጨዋወት የተመለከቱት የብቃት ችግር፤ የወኔ መቀዝቀዝ እና ያለጎል የደረሰው ተከታታይ ሽንፈት አንገታቸውን አስደፍቷል፡፡ መከፋታቸውንም በተለያዩ መንገዶች ገልፀውታል፡፡ በአሰልጣኙ ብቃት እና ተጨዋቾችን የመቀየር ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያላቸውም ብዙዎች ነበሩ፡፡ በአጥቂ በተከላካይ መስመር ተሰላፊ የሆኑ ተጨዋቾች ባሳዩት አቋም ተናድደው ተጨዋቾቹን ያወገዙም ጥቂት አይደሉም፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዋልያዎቹ ባስመዘገቡት ውጤት ተነሳስቶ የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተመልሶ እንዳያሽቆለቁል በመስጋት የተለያዩ ሃሳቦችን አንፀባርቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የ2014 የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጉዞውን ከ2 ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ከጀመረበት  ጨዋታ አንስቶ የሚገርም ድጋፍ እየሰጡ ነበር፡፡ ከቻን ውድድር የምድብ መጨረሻ ጨዋታ በኋላ ግን ድጋፉ ወደ ብስጭት እና ተስፋ መቁረጥ ተቀይሯል፡፡ ዋልያዎቹ በደቡብ አፍሪካ በነበራቸው ጉዞ በዚያው አገር በተለያዩ ግዛቶች ያሉ ኢትዮጵያውያንን ለድጋፍ በማስተባበር ከፍተኛ ሚና የነበረው ወጣት ፅኡመልሳን ውብሸት ይባላል፡፡ የቀበናው ልጅ  ፅዑመ በደቡብ አፍሪካ መኖር ከጀመረ ከ14 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡  
ይህ ማለት ከእግር ኳስ በተያያዘ ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለድጋፍ በማስተባበርና የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ታዋቂ ሆኗል። ‹ብሄራዊ ቡድናችን በደቡብ አፍሪካ በተለያዩ ውድድሮች ሲያሸንፍ ለማየት ባንታደልም በነበረው ጉዞ ያን ያህል አናዝንም›› ይላል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዋልያዎቹ ከዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያና ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ በቻን በተሻለ ጥንካሬና ብቃት የሚመጡበትን ቀን በተስፋ ሲጠባበቁ እንደነበር ያስታወሰው ፅዑመ፤በቻን ውድድር ብሄራዊ ቡድኑ ከምድቡ በጊዜ ሲሰናበት ደንግጠናል ብሏል፡፡ “ዋልያዎቹ በቻን ተሳትፏቸው መልካም ውጤት ይኖራቸዋል ብለን ስንጠብቅ በተጋጣሚዎቻቸው ብልጫ ተወስዶባቸው እና ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ስንመለከት ምን ጎደላቸው ብለን ግራ ተጋብተን ነበር ያለው ፅዑመ፤ ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ከማንኛውም አገር የሚስተካከል አቅም እንዳላት እናምናለን፤ በስፖርቱ የሚገኝ ውጤት ለሁላችንም ኩራት ነበር፡፡ የአገራችንን ገፅታ በመገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ይገባናል፡፡ ስለዚህ ለወደፊቱ መሰረታዊ የእድገት ስራዎች ለውጥ ማየት እፈልጋለሁ” ብሏል፡፡ በ1990ዎቹ አጋማሽ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በታዳጊ ፕሮጀክት በመስራት እና የተለያዩ አዝናኝ የእግር ኳስ ውድድሮችን በማዘጋጀት የሚታወቀውና አሁን በደቡብ አፍሪካ በንግድ ስራ የተሰማራው አቶ ኤልያስም ለወደፊቱ ምን መደረግ እንዳለበት አስተያየት ሰጥቷል፡፡  በበኩሉ የኢትዮጵያ ቡድን በአለምአቀፍና በአህጉራዊ ደረጃ በሚሳተፍባቸው ውድድሮች ብቁ ተፎካካሪ እንዲሆን በወጣቶች እና በታዳጊዎች የፕሮጀክት እንቅስቃሴዎች በስፋት መስራት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነም ይመክራል፡፡ በአመራር ላይ የሚገኘው የእግር ኳስ ፌደሬሽን  በረጅም ጊዜ እቅድ የሚሰራበትን ስትራቴጂ በመቀየስ እና ሳይንሳዊ የስልጠና መንገዶችን በመቅረፅ መስራት አለበት ብሎ አስተያየት ሰጥቶናል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ አቅጣጫ ትኩረት በማድረግ ከ15 እና ከ17 አመት በታች በሚደረጉ አህጉራዊ ውድድር በመሳተፍ ካልሰራች በዋና ብሄራዊ ቡድን ዘላቂ የሆነ ብቃት እና ውጤታማነት ለማግኘት ይከብዳታልም ብሏል፡፡  
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ማናጀር የሆኑት አቶ ሳምሶን ጌታቸው ይህን አስመልክቶ በሰጡን አስተያየት፤ በአገሪቱ ከ15 ዓመት በታች ላለው የታዳጊ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚሆን የአምስት አመት የገንዘብ ድጋፍ ከኮካ ኮላ ኩባንያ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ለዚሁ ተግባር ከኮካ ኮላ በየአመቱ የሚሰጠውን የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ በየክልሉ በሚደረጉ የታዳጊዎች ውድድር ላይ በመበጀት እንዲሠራ ታስቦ ለፌዴራል ስፖርት ኮምሽን የፕሮጀክት ስምምነቱ እንደቀረበ እና ለተግባራዊነቱ የኮሚሽኑ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከ17 ዓመት በታች ባሉ ወጣቶች ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየሰራ እንደሆነ የሚናገሩት  የፌዴሬሽኑ የውድድር እና ስነስርዓት ዲያሬክቶሬት አቶ ተድላ ዳኛቸው ናቸው፡፡  በ11 የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከ17 ዓመት በታች ውድድርን ለማስጀመር  ዝግጅቱን ጨርሰናል ያሉት አቶ ተድላ፤  የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ ሁሉም ክለቦች ተገቢውን የእድሜ ምርመራ አድርገው በውድድሩ እንዲሳተፉ መመሪያ ተሰጥቶ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

የጌታነህ ምክር
ጌታነህ ከበደ በጆሃንስበርጉ ቢድቬስት ዊትስ ዩንቨርሲቲ ክለብ መጫወት ከጀመረ ሁለት ወራት ሆኖታል፡፡ አጥቂው ጌታነህ ከበደ ለዚሁ ክለብ 5 ጐሎችን በማስቆጠር በደቡብ አፍሪካ ሚዲያ ተደንቋል፡፡ ዋልያዎቹ ከሊቢያ አቻቸው ጋር በፍሪስቴት ስታዲየም ያደረጉትን ጨዋታ እንደተመለከተ የነገረን ጌታነህ ቡድኑ የግብ አጋጣሚዎች ሊጠቀም ባለመቻሉ ለሽንፈት እንደሚጋለጥ ይናገራል፡፡ ጌታነህ ከበደ በደቡብ አፍሪካው ክለብ መጫወት ከጀመረ በኋላ ብዙ ለውጥ ይታይበታል የሚታየውን የአካል ብቃት ችግር እያለፈው እንደሆነ ታዝበናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ያለባቸው የአካል ብቃት ችግር በጂም በሚደረጉ ልምምዶች እና ስልጠናዎች ሊስተካከል እንደሚችል በጌታነህ ከበደ መለወጥ አረጋግጠናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቻን ውድድር ከምድብ ማጣርያ በጊዜ መሰናበቱ እንዳስከፋው የገለፀልን ጌታነህ ፤ የአገራችን ክለቦች በአደረጃጀታቸው ፕሮፌሽናል ደረጃዎችን በማሟላት ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያስፈልጋቸው፤ በባላሃብቶች ከፍተኛ ድጋፍ አግኝተው መሰረታዊ የስልጠና መሰረተልማቶች ማስፋፋት እንዳለባቸው እና በታዳጊ ፕሮጀክቶች በስፋት መሰራት እንደሚያስፈልግ ምክሩንም ለግሷል፡፡

የሰውነት ቢሻው መጨረሻ
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ብሄራዊ ቡድናቸው የመጨረሻውን የምድብ 3 ጨዋታ ከጋና አቻው አድርጎ 1ለ0 ከተሸነፈ በኋላ  ከአምበሉ አዳነ ግርማ ጋር በፍሪስቴት ስቴት ስታድዬም የፕሬስ ኮንፍረንስ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ  ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ መግለጫ ላይ ከኮንጎ እና ከጋና ጋር በተደረጉ ሁለት ግጥሚያዎች ዋልያዎቹን በአምበልነት የመራው አዳነ ግርማ ቡድኑ ስለነበረው የጎል ማግባት ችግር ሲጠየቅ ‹‹በመከላከል ረገድ እንደ ቡድን ጥሩ ብንቀሳቀስም፤ በማጥቃት ጨዋታ ላይ በቡድን አለመስራታችን ዋጋ አስከፍሎናል›› ሲል ተናግሯል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው ብሄራዊ ቡድናቸው በቻን ላይ በነበረው ተሳትፎ ደስተኛ እንዳልነበሩ ሲናገሩ፤ ከውድድሩ ብዙ ትምህርት እና ልምድ ማግኘታቸውን ገልፀዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቀጣይ ጉዞ እና በዋና አሰልጣኝነት ስለመቀጠላቸው ወይም ስለመልቀቃቸው ከስፖርት አድማስ ግልፅ ማብራርያ እንዲሰጡም ተጠይቀው ነበር፡፡ በምላሻቸው ‹‹ብሄራዊ ቡድኑን ማሰልጠኔ አብቅቷል ብዬ አልተናገርኩም። አሉባልታው ከየት እንደመጣ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ያለኝ ብቸኛ ሙያ ነው፡፡ ካለሰለጠንኩ ምን ልሰራ እንደምችል አላውቅም፡፡ የእኔ አላማ በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በመቀጠል እግር ኳሱን በማሻሻል ለመስራት ነው፡፡ እግር ኳስ በስህተት የተሞላ ነው። ቡድናችን በማጥቃት እና በመከላከል ያሉበት መሰረታዊ ችግሮች ዋጋ አስከፍለውታል። ከቻን በኋላ ስራችንን የምንቀጥለው ለብሄራዊ ቡድኑ ተተኪ የሚሆኑ ወጣት እና ተሰጥኦ የያላቸውን ተጨዋቾች በማፈላለግ ተግባራት ላይ በማተኮር ነው፡፡
በአጠቃላይ የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ሙያዬ እንደመሆኑ ስራዬን አቆማለሁ ብዬ አላስብም፡፡ ግን አይታወቅም፤ ስራዬን እንድለቅ የሚያደርግ አስገዳች ሁኔታ እና ተፅእኖ ካልተፈጠረ በቀር›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቡድናቸውን ለቻን ውድድር እንዴት እንዳዘጋጁ፤ ከውድድሩ ምን እንደተማሩ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችንም በጋዜጣዊ መግለጫው ምላሽ እንዲሰጡባቸው የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጋዜጠኞችም  ጠይቀዋቸዋል፡፡ ‹‹የተዘጋጀነዉ ለ15ቀናት ነው፡፡
የአካል ብቃት ልምምድ ለማድረግ በቂ ግዜ ባይኖረንም  ሁሉንም ስራ አሰርቻለሁ፡፡ አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ከማድረግ ባሻገር በዝግጅታችን የነበረው የማቀናጀት ስራ ነዉ፡፡ በአጠቃላይ በቻን ተሳትፎ የኛ ተጫዋቾች ከሌሎች ሀገር ተጫዋቾች በተለየ የሚጎድሏቸውን ብቃቶች ታዝብያለሁ፡፡ በእኛ  እና በሌሎች  ተጫዋቾች ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ባይኖሩም በሊግ ተጫዋቾች መሀል ያለዉን ልዩነት በሚገባ ተመልክቻለሁ›› በማለት ሰውነት ቢሻው የቻን ውድድርን ተሰናብተዋል፡፡

Monday, 27 January 2014 08:40

አደገኛው ውሻ!

አለሙ ገዳ እሳት የላሰ ደላላ ነው፡፡ አንደበተ ርዕቱ-አፈ ቅቤ፡፡ ልበ ምላጭ፡፡  ወደሚከራየው ቤት አቀናን፡፡ ከእርምጃውም ከምላሱም እየፈጠነ… “አሁንም ሌጣ ወንደላጤ ነህ! አግባ አግባ እንጂ…. እኔ ጣፋጭ የትዳር ሕይወትን አጣጥሜለሁ፡፡  ነገር ግን ምን ያደርጋል አምና ባለቤቴ ወደ ሳውዲ ተሰደደች “ባስና ሴት ጥለውኝ ሄዱ ብለህ አትዘን ከሳውዲ እየገቡ ነው” የሚል ጥቅስ አንብቤ ከዛሬ ነገ ትገባለች በሚል እየጠበኳት ነው፤ እንደመጣች ወዲያውኑ ቀብድ አስይዛታለሁ”
ግር ብሎኝ “ቀብድ አስይዛታለሁ” ስትል?­
“አስረግዛታለሁ ማለቴ ነው….ግን ምን ዋጋ አለው የሳውዲ ተመላሽ ሴቶች አብዛኛዎቹ አርግዘው ነው የሚመለሱት… ያ! ሁሉ የበረሃ… የባህር ላይ ጉዞ ለእርግዝና ነው እንዴ ያስብላል… ለነገሩ ንግስት ሳባ ያንን እልህ አስጨራሽ የእስራኤል ጉዞ አድርጋ አርግዛ አይደል የተመለሰችው” ሲል የነገር መአቱን እንደ ዶፍ አወረደው ….
“ወደ መካከለኛ ምስራቅ የሚደረጉ ጉዞዎች በእርግዝና የመጠናቀቅ እድላቸው የሰፋ ነው፡፡ ዛሬም ሆነ በዘመነ ሳባ ጥንትም…. እናም የሳውዲ ተመላሾች ዳፋ ቤት ኪራይን እሳት አደረገው  አንተ እድለኛ ነህ በ900 ብር …”
የአለሙ ገዳ ስለ ትዳሩ አቆራቆር…. የሚስቱ ስደት… የንግስት ሳባ ጉዞ… ዝባዝንኬ የቤት ኪራይ መናር ላይ ጉብ ለማለት ነው…  በዚህም ቢያንስ የ300 ብር ፈርቅ በእኔ ላይ ይይዛል…
“እየደረስን ነው… መታጠፊያው ላይ ያለው ቀይ በር ሰፊ ግቢ ነው … ባህር ዛፍ፣ ጽድ፣ በእንጆሪ ዛፎች የተዋበ ኤደን ገነት ግቢ ውስጥ ነው የማስገባህ …”
ደረስን፡፡ በሩ ላይ “ከአደገኛ ውሻ ተጠንቀቁ” የሚል በጉልህ ተፅፏል፡፡ ቅስሜ ስብር አለ፡፡ ውሻ ያለበት ግቢ መግባት እንደማልፈልግ ነገርኩት፡፡ …. ውሻው ሁሌም በሰንሰለት እስር ላይ ነው፡፡ አይደርስብህም ….  አልፎ አልፎ ቅንጣቢ ስጋ ጣል ብታደርግለት ይላመድሃል…
ወደ ግቢው ዘለቅን፡፡ አለሙ ገዳ የደሰኮረው የእንጆሪ፣ የጽድ ዛፎች ግቢው ውስጥ ለመሃላ አይታዩም፡፡ ጉቱ መሳይ የደረቁ ባህር ዛፎች… በሞትና ሕይወት መካከል ጣር ላይ ያሉ የወየቡ ኮባዎች፣… አዛባ አዛባ የሚሸት የጠቆረ ውሃ ግቢውን አቋርጦ ያልፋል… ድንቄም ኤደን ገነት፡፡
ዋናው ቤት በረንዳ ላይ ወጠምሻ ጐረምሳ፣ ሴት ጭን መሐል ገብቶ ሹርባ እየተሰራ ነበር፡፡ “ቤት ለመከራየት ነው አይደል! አባዬን ልጥራው” ብሎ ብድግ አለ፡፡ አፍታም ሳይቆይ መለስ አለና “ይመጣል” ብሎን ወደ ሽሩባ ሰሪዋ ራመድ ሲል … ጭኗን ፈርከክ አደረገችው- ቀይ ጭኗ ላይ የእኔም የአለም ገዳ አይኖች እንደ ማስትሽ ተጣበቁ፡፡ ወጠምሻው እንደሶኬት ጭኖቿ መካከከል ተሰካ፡፡
አለሙ ገዳ በማንሾካሾክ ድምጽ “አይተሃታል ጭኗን በልቀጥ ስታደርገው…በልቃጣ ብልቅጥቅጥ… እሱም እንደ ሳንዱች ሄዶ ውትፍ! የዘቀጠ … አውቃታለሁ… አለሌ ሸርሙጣ ናት!
“ምን ታደርገዋለህ ሥራዋ ነው” አልኩት፡፡
“የምን ሥራ! ሥሪያ ነው የያዙት”
… ቤት አከራዩ አዛውንት ከእሳቸው ጋር አብራ ያረጀች የምትመስል መነጽራቸውን አውጥተው ደስ በማይል አተያይ አዩኝ- ማለትም ገላመጡኝ፡፡ ለወደፊቱ እንድፈራቸው ተጽእኖ ለመፍጠር ይሆን? የእዛኑ እለት ዕቃዬን አስገባሁ፡፡ ቀፎው አምፖል አልባ በመሆኑ ወጣ ብዬ አምፖል ገዝቼ ለመግጠም ወንበር ላይ እንደቆምኩ አከራዩ ወደ ክፍሌ ገባ፡፡ “ላላ አድርገህ ግጠመው- አጥብቀህ ከገጠምከው ያለውን ኃይል ሁሉ ምጥጥ አድርጐ ነው የሚበላው….”
ስንት ጉድ ይሰማል ሰዎች- ምንስ ተብሎ ይመለሳል፡፡ እኝህን ሰው መጠንቀቅ እንዳለብኝ እያሰብኩ ወደ እንቅልፍ…
ታህሣሥ 0 2ቀን 2006 ዓ.ም …
ትንሽ አመሻለሁ- በመጠኑ ለመቀማመስ፡፡ ወደ አራት ሰዓት በሩን ከፍቼ ስገባ ውሻው አንባረቀብኝ። የነጐድጓድ ያህል! የታሰረበት ስንሰለት ረዥም በመሆኑ ወደ እኔ ተወነጨፈ፡፡ ሰንሰለቱ ላለመበጠሱ ምን ዋስትና አለኝ፡፡ ወደ ክፍሌ ተወነጨፍኩ፡፡ በበሩ ሽንቁር ሳይ ወደል ጥቁር ውሻ!!
ታህሣሥ 03 ቀን 2006 ዓ.ም …
4፡30 ወደ ግቢ ገባሁ፡፡ ወደሉ ውሻ ጥግ ይዟል። ምንም ድምጽ አላሰማም፡፡ ክፍሌ ልደርስ ስል እየጮኸ ወደ እኔ ተወነጨፈ፡፡ ዱብ ዕዳ! ብርክ ያዘኝ። እንዴት በሬን ከፍቼ እንደገባሁ አላስታውስም። በድንጋጤ ቀልቤና ስካሬ ተገፈፈ፡፡ “ለምን አሳጥረው አያስሩትም” በረዥም ሰንሰለት የመታሰሩ ሚስጥር የተወሰነ ሜትሮች እንዳሻው እየተወነጨፈ፣ የሰውን ቆሌና ስካር ለመግፈፍ ይሆን? … ይህንን የሚያውቁት ሰይጣንና መሰሪው አከራይ ናቸው፡፡ እዚህ ሲዖል ግቢ ውስጥ ያስገባኝን የአለሙ ገዳ ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለብኝ- ለአደገኛው ወደል ጥቁር ውሻ ቅንጥብጣቢ ስጋ ጣል ማድረግ…!
ታህሣሥ 04 ቀን 2006 ዓ.ም
4፡30 ከግሮሰሪ ወጣሁ፡፡ 5፡00 የፊት ለፊቱን በር ከፍቼ ገባሁ፡፡ ውሻው በጩኸት ተቀበለኝ፡፡ ቅንጣቢ ስጋ ወረወርኩለት፡፡ ስጋውን ትቶ “አንተን ነው መብላት የምፈልገው” በሚል ዓይነት ጩኸቱን ለቀቀው፡፡ ወደ ክፍሌ ገብቼ በበሩ ቀዳዳ ሳየው ስጋውን ዋጥ ስልቅጥ ሲያደርግ አየሁት፡፡
ታህሣሥ 05…. የወረወርኩለትን ስጋ ትቶ እኔው ላይ ማላዘኑ እንደቀጠለ ነው …
ታህሣሥ 06… ሙዳ ሥጋ ወረወርኩለት- በስሱ ጮኸብኝ፡፡
ታህሣሣ 07… በውድቅት ሌሊት ነበር የገባሁት… የወረወርኩትን ሥጋ እና አጥንት ከመቆረጣጠም ውጪ አንዳችም ድምጽ አላሰማም፡፡ “ተመስገን በመጨረሻ ተላመደኝ”
ታህሣሥ 08… ሙዳ ስጋ ወረወርኩለት፤ ስጋውን ከመብላት ውጪ ጸጥ ረጭ…!
ታህሣሥ 09 ቀን 2006 ዓ.ም …
ከምሽቱ 5፡00 ከግሮሰሪ ወጣሁ፡፡ 5፡30 የፊት ለፊቱን በር በሰረገላ ቁልፍ በመክፈት ላይ እያለሁ ለውሻው ምንም አለማያዜ ትዝ አለኝ፡፡ በሩን ከፍቼ ገባሁ፤ ወደ ክፍሌ ራመድ አልኩ… “ውሻው ይጮህብኝ ይሆን?” በሚል ስጋት ዞር ብዬ አየሁት- በለሃጭ ተዝረብርቧል፡፡ የሰረገላ መንቋቋት-ጂን! ጂን! የሚል የሰካራም ትንፋሽ /stimulus/ የውሻው ለሀጭ /Response/ የፖቭሎቭ ቲዎሪን በዛ ምሽት በአይኔ ለማየ በቃሁ፡፡ ውሻው አንዳችም ድምጽ አላሰማም፡፡
ታህሣሥ 10 ቀን 2006 ዓ.ም…
ከምሽቱ 5፡00፡፡ አራተኛ ደብል ጅን ላይ ስደርስ፣ ለውሻው ምንም ነገር ይዤ ላለመግባት ወሰንኩኝ። የጠጣሁት ጅን ድፍረት ሰጥቶኛል፡፡ ወደ ኋላ ዞር ሳልል በቀጥታ ወደ ክፍሌ ገባሁ- ውሻው አንዳችም ድምጽ አላሰማም፡፡
ታህሣሥ 11… ከምሽቱ 5፡30 ገባሁ፡፡ ጢው ብዬ ሰክሬአለሁ፡፡ “ደቼ ብላ!” ብዬ ውሻውን ተሳድቤ ወደ ክፍሌ ገባሁ፡፡ ውሻው ድምጽ አላሰማም፡፡
ታህሣሥ 12 ቀን 2006 ዓ.ም በውድቅት ሌሊት ነበር የገባሁት፡፡ እየተደነቃቀፍኩ ወደ ክፍሌ ስስገመገም ውሻው ግቢውን በጩኸት ቀውጢ አደረገው፡፡ ሰንሰለቱን ለመበጠስ ተውተረተረ። ጩኸቱ እንደ ነጐድጓድ ተስገመገመ፡፡ በፍጥነት ወደ ክፍሌ ገብቼ በሬን ጥርቅም አድርጌ ዘጋሁት። በመሐል ውሻው ጸጥ ረጭ አለ፡፡ በግማሽ ስካር እና እንቅልፍ መሐል ስለነበርኩ፣ በዚያች ቅጽበት ያሰብኩት ውሻው በምትሃት በሁለት እግሩ ተራምዶ በእጆቹ ያንኳኳ ነው የመሰለኝ፡፡ … በሩን አስከፍቶ ሊዘነጣጥለኝ.. ይመስገነው አከራዩ ነበር፡፡ ወቀሱኝ.. “ለምን እንዲህ ታመሻለህ? እኛንም ረበሽከን-በደረቅ ሌሊት በመግባትህ ነው ውሻው እንኳን ተበሳጭቶ የሚጮኸው”! የእኔ ማምሸት  ውሻውን የማበሳጨቱ ነገር እየገረመኝ ይቅርታ ጠየቅኋቸው፡፡ ከአከራዩም ሆነ ከውሻው ጋር ሰላም ለመፍጠር መላው ገብቶኛል።
ታህሣሥ 13 ቀን 2006…
ያለፋትን 4 ቀናት ለማካካስ ወፈር ያለ ሙዳ ስጋ ይዤ ገባሁ፡፡፡ በሩን በቀስታ ከፍቼ ውሻው ከመጮሁ በፊት በፍጥነት ሥጋውን ወረወርኩለት… ጮኸብኝ! ሰንሰለቱን ለመበጠስ እየታገለ አላዘነ፡፡ ስጋውን እልህ ይዞት አይበላ ይሆን? በሚል በበሬ ሽንቁር አይኔን ላኩኝ፡፡ ዋጥ ስልቅጥ እያደረገ ነው - “አፈር ብላ!” …
ታህሣሥ 14…. ሙዳ ስጋ ጣል ባደርግለትም ግቢውን በጩኸት ቀውጢ አደረገው፡፡
ታህሣሥ 15… ከቅንጥብጣቢ ሥጋ በተጨማሪ አጥንት ቀላቅዬ እነሆ ብለው እየጮኸ፣ እኔኑ ለመንከስ ከሰንሰለቱ ጋር ትንቅንቅ ያዘ….
ታህሣሥ 16… የወረወርኩለትን ሙዳ ሥጋ ከመሰልቀጥ ውጭ አንዳችም ድምጽ አላሰማም። በእኔ እና በውሻው መካከል የተፈጠረውን ሰላም ላለማደፍረስ ቃል ገባሁ፡፡
ታህሣሥ 17 ቀን 2006 ዓ/ም …
ጂን በቶኒክ እየተጐነጨሁ ነው፡፡ ስለዚያ ወደል ጥቁር ውሻ እየቆዘምኩ ነበር፡፡ እስከ መቼ ድረስ ከርሱን ስሞላ እኖራለሁ፡፡ ለአከራዩ ስሞታ ማቅረብ ትርጉም የለውም፡፡ “በውድቅት ስለምትገባ ተበሳጭቶ ነው የሚጮኸው”? የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡኝ …
… እንደገባሁ ቁራጭ ቅንጣቢ ሥጋ ወረወርኩለት። በፍጥነት ዋጥ ስልቅጥ አድርጐ አይኖቹን  አጉረጠረጠብኝ … እኔኑ ሊሰለቅጠኝ ይሆን ?
በመሰላቸት እየታከተኝ ወደ እንቅልፍ አለም… በዚያው ወደ ቅዠት ይሁን ሕልም …
መንገድ ጠርዝ ታክሲ እየጠበቅሁ፣ ባለ ዲኤክስ ሊፍት ሰጠን፤ ሶስት ሰዎች ገባን፡፡ ጉዞ ጀመርን። ሹፌሩ “እኔ ሊፍት ላለመስጠት ምዬ ነበረ… ለዚህ ያበቃኝ ደሞ አንዱን ሊፍት ሰጥቼው፣ ለውሻዬ እራት የገዛሁትን ግማሽ ኪሎ አጥንት ይዞብኝ ወርዶ ነው … ቤት ስደርስ ለውሻዬ ምን ልስጠው? ጾሙን አደረ” … ሁለቱ ወረዱ፡፡ ጉዞአችን ቀጠለ፡፡ ሹፌሩ ወደ እኔ ዞር አለና “የውሻዬን እራት የበላኸው አንተ ነህ! ያኔ አራቱን በልተህበታል! ዛሬ በተራው አንተኑ ይበላኸል!” የነዳጅ መስጫውን ረገጠው፡፡ መኪናዋ እንደ ጥይት ወደፊት ተተኮሰች፡፡ ብርግድ ብሎ በተከፈተ በር ገብታ ቀጥ ብላ ቆመች… እንዴት ከመኪናዋ እንደወረድኩ ሳላውቀው በዚያው ቅጽበት ወደል ጥቁር ውሻ ሰንሰለቱን በጥሶ ወደ እኔ ሲወነጨፍ… ጩኸት አሰምቼ ከእንቅልፌ ብንን አልኩ፡፡
በእውኔም ሆነ በሕልሜ ሕይወቴን ወደ ሰቅጣጭ ትራጀዲ የለወጠውን ወደል ጥቁር ውሻ ለመገላገል ስል በነገው ዕለት ቤቱን ለመልቀቅ ወስኛለሁ፡፡  

Published in ልብ-ወለድ

             ሰሞኑን በጐንደር ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ የተለያዩ ዝግጅቶች ተካሂደዋል፡፡ ዓመታዊው “የባህል ሳምንት” አካል የሆነው የባዛር ዝግጅት ተጠቃሽ ነው፡፡
ባዛሩን ስጐበኝ ነበር የጐንደር እህት ከተማ ከሆነችው የፈረንሳይዋ ቬንሰን ከተማ ጥልፍ ለመማር የመጣውን  የ21 ዓመት ፈረንሳዊ ወጣት ያገኘሁት፡፡ እድሪያን ይባላል፡፡ እንዴት ወደ ጐንደር እንደመጣ፣ የጥልፍ ሙያ ለመማር  ምን እንዳነሳሳውና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተን ተጨዋውተናል፡፡ እነሆ:-
መቼ ነው የመጣኸው?
ሶስት ሳምንት ሆኖኛል፡፡
የመጣህበት ዋና ጉዳይ ምንድን ነው?
በዋናነነት የመጣሁት ጥልፍ ለመማር ነው፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደሰማሁት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሚጐበኙ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ ጐንደር ውስጥ የፋሲል ግንብና ሌሎች ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ በተለይ ቬንሰን የጐንደር እህት ከተማ ከሆነች በኋላ ስለጐንደር ብዙ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እግረ መንገዴን ለጉብኝትም ጭምር ነው የመጣሁት፤ በዋናነት ግን ጥልፍ ለመማር ነው፡፡
አሁን ያገኘሁህ ጥልፍ እየተለማመድክ ነው …. መቼ ጀመርክ?
ጥልፍ በራሴ መንገድ መለማመድ የጀመርኩት ፈረንሳይ እያለሁ ከአንድ አመት በፊት ነው፡፡ በአገሬ የዲዛይን ስራዎችን መስራት ከጀመርኩ በኋላ ማለት ነው፡፡ በተለያዩ ጅንስ ሱሪዎች እና ሸሚዞች ላይ የተወሰኑ የጥልፍ ዲዛይኖችን እሰራለሁ፡፡ ለምሳሌ የመስቀል ዲዛይን ለመስራት ሁሌ ነጥቦችን በክብ በክብ እሰራና እሱን እጠልፈዋለሁ፡፡ ግን ሁሌ አንድ አይነት ነው፡፡ በክብ ብቻ ነው መስቀል የምሰራው፡፡
ጥልፍን ለመማር የመረጥክበት ዋናው ምክንያት ዲዛይነር ስለሆንክ ነዋ?
አዎ! በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጣሁ በኋላ ያየሁት የጥልፍ አይነት ብዙ አይነትና የተለያየ ዲዛይን ያለው ነው፡፡ ለምሳሌ ይህን መስቀል ተመልከቺው (የአበሻ ልብስ ላይ እየጠለፈ ያለውን መስቀል እያሳየኝ) በተለያየ መልክ የመስቀል ቅርጽ መጥለፍ ይቻላል… ይህን በማወቄ ያስደስተኛል። አሁን ጥሩ እየለመድኩ ነው፡፡ ወደ አገሬ ስመለስ ይህን ባህላዊ ጥልፍ ዘመናዊ ልብሶች ላይ በመጥለፍ ትልቅ ባለሙያ የመሆን እቅድ አለኝ፡፡ ፕሮጀክት ነድፌ ስራዎቼንም በኤግዚቢሽን መልክ አቀርባለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ አስተማሪዬ ጐበዝ ሴት ናት፤ በደንብ እያስተማረችኝ ነው፡፡
የመጀመሪያ ሙያህ ምን ነበር?
የመጀመሪያ ሙያዬ ሙያ ከተባለ ማክዶናልድና ሳንዱች አብሳይ ነበርኩኝ፡፡
ይሄን ሙያህን አልወደድከውም?
ምን መሰለሽ? ሳንዱች ማብሰል፣ ማክዶናልድ መስራት …. በቃ ሌላ አዲስ ነገር የለም፤ ሁሌም ተደጋጋሚና አሰልቺ ነው፡፡ በመጀመሪያ የምወደው ስራም አልነበረም፡፡ አሁን ያለሁት መስራት የምፈልገው ሙያ ጅማሮ ላይ ነው፡፡ በዚያ አሰልቺ ህይወት ውስጥ መቆየት አልፈልግም፡፡
በሳንዱችና በማክዶናልድ አዘጋጅነትህ የተዋጣልህ ነበርክ?
በጣም ጐበዝ ነበርኩኝ፤ ስራውን ባልወደውም።
አንተና አስተማሪህ በምን ቋንቋ ትግባባላችሁ?
እኔ “ትንሽ” ፣ “ትልቅ”፣ “አመሰግናለሁ”፣ “እሺ”… የሚሉትን ለመግባቢያ የሚሆኑ የአማርኛ ቃላትን እናገራለሁ፤ አስተማሪዬም ትንሽ ትንሽ እንግሊዝኛ ትችላለች፡፡ አንዳንዴ ሲያቅተን በምልክትም እንግባባለን፤ በአብዛኛው በተግባር የምታስተምረኝ ይበልጣል፤ እስካሁን ለመግባባት አልተቸገርንም፡፡
ከዚህ በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተህ ታውቃለህ?
አልመጣሁም፡፡ ኢትዮጵያም ጐንደርም ስመጣ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
ከጥልፍ አስተማሪህ ጋር እንዴት ተገናኛችሁ?
ብዙ ጥልፍ የሚጠልፉ ሰዎችን አየሁና እሷ ጋር ሄጄ ጥልፍ ታስተምረኝ እንደሆነ ጠየቅኋት፤ እሺ አለችኝ፡፡ ሳያት ከሌሎቹ እሷ ጐበዝ ናት፤ በደንብ ትጠልፋለች፡፡ በዚህ መልኩ ጀመርኩኝ …፡፡
ወደ አገርህ ስትመለስ ለራስህ በልብሶች ላይ ከመጥለፍ ባሻገር እውቀትህን ለሌሎች ለማስተላለፍ አላሰብክም?
ጐንደር ውስጥ በሚኖረኝ ቀሪ ሶስት ሳምንት፣ ጐበዝ የጥልፍ ባለሙያ እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ። ቅድም እነደ ነገርኩሽ ዘመናዊና ባህላዊ ልብሶችን በጥልፍ የማሳመር እቅድ አለኝ፡፡ ከዚያ በተረፈ በማቀርበው ኤግዚቢሽንና በስራዬ የሚመሰጥ ካለ እውቀቴን አካፍለዋለሁ፡፡ የራሴ ከተማ ቮንሰን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገሮች ግንኙነቶችና ትውውቆች  ስላሉኝ ሙያውን የማስፋፋት እቅድ አለኝ፡፡ ለምሳሌ እንደነ ቬትናም ባሉ አገሮች የማውቃቸው ሰዎች አሉ በእነሱ አማካኝነት ሙያውን የማስተዋወቅና የማስተማር ፍላጐት አለኝ፡፡
የፋሲልን ግንብ ጐበኘህ?
በደንብ ጐብኝቻለሁ፡፡
እንዴት አገኘኸው?
በጣም አሪፍ ነው፡፡ በወሬ ከምሰማውም በላይ ነው የሆነብኝ፡፡ የተገነባበት ዘመን ረጅም እንደመሆኑ ያለው አጠቃላይ የሥነ ህንጻ ዲዛይን አስገርሞኛል፡፡
ኢትዮጵያ እንደመጣህ መጀመሪያ የበላኸው ምግብ ምንድነው?
ፍርፍር ዳቦ
ዳቦ ፍርፍር ማለትህ ነው?
እኔ ያልኩትና አንቺ ያልሽው ልዩነት አለው እንዴ?
የለውም ግን አጠራሩ እኔ ባልኩት መንገድ ይሻላል ብዬ ነው፡፡
ሶሪ… ምግቡ ግን አንድ ነው አይደለ?
አዎ፤ አንድ ነው፡፡ ሽሮ ወጥ፣ ዶሮ፣ ክትፎ… እኒህን ባህላዊ ምግቦችሽ አልቀመስክም?
ያልሻቸውን ምግቦች ቀምሻለሁ፤ ኧረ ፊልተር የሚባል ባህላዊ መጠጥም ጠጥቻለሁ፡፡ የአትክልት ሾርባችሁን ወድጄዋለሁ፡፡ ብቻ ሰውም አገሩም ጥሩ ነው፤ ደስ ይላል፡፡
አየሩስ ተስማምቶሃል?
እስካሁን ያስቸገረኝ ነገር የለም፤ እንደምታይኝ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለሁት፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰህ የምትመጣ ይመስልሃል?
በተደጋጋሚ የምመጣ ይመስለኛል፡፡ የአሁኑ አመጣጤ ቀጥታ ጐንደር ነው፤ ለጥልፉ ትምህርት።  ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሚጐበኙ ማራኪ ቦታዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ መጐብኘት እፈልጋለሁ፡፡

Published in ጥበብ

‘አንጀሊና ጆሊ’ የሚለው ስም፣ አሁንም ከኢትዮጵያ ጋር ተያይዞ ተነሳ፡፡ አሁንም በስፋት ተዘገበ፣ በብዙዎች ተሰማ፣ ብዙዎችን አነጋገረ፡፡ አሁን ይሄን ታዋቂ ስም ከኢትዮጵያ ጋር አያይዞ ያስነሳው፣ ያ የፈረደበት ማደጎ አይደለም፡፡ በሁለቱ መካከል ትስስር የፈጠረችው፣ ከአመታት በፊት ወደ አሜሪካ በማደጎ የተወሰደችው ዘሃራ አይደለችም - አበራሽ እንጂ፡፡ ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኝ አንዲት የገጠር መንደር ውስጥ ተወልዳ ያደገች የ14 ዓመት ልጃገረድ ናት- አበራሽ በቀለ፡፡
አበራሽንና አንጀሊናን ምን አገናኛቸው?... ህይወት!...
ከአመታት በፊት…
የገጠሯ ጉብል አበራሽ፣ አንድ ማለዳ ደብተሮቿን ሸክፋ ከጎጆዋ በመውጣት፣ ከመንደሯ ርቆ ወደሚገኘው ትምህርት ቤቷ የእግር ጉዞ ጀመረች፡፡ ዳገት ቁልቁለቱን እየወጣች እየወረደች ወደ እውቀት ቤቷ ፈጥና ለመድረስ ረጅሙን መንገድ ተያያዘችው፡፡ እንዳሰበችው ፈጥና ለመድረስ፣ ድካሟን ተቋቁማ ነጠቅ ነጠቅ ብላ መራመድ ይኖርባታል፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ቤቷ ለመድረስ ገና ብዙ መንገድ ይጠብቃታል። ምክንያቱም እሷ እንደ ሰውየው ፈረስ የላትም - ዳንግላሳ እየጋለበ ከጥሻው ስር ብቅ ሲል እንዳየችው ሰውዬ!!...
አበራሽ ጉዞዋን ትታ በፈረሰኛው የምትቀናበት ጊዜ የላትም፡፡ እየረፈደ ነው፡፡ ስለዚህ ፍጥነቷን ጨምራ መጓዝ አለባት፡፡ ጉዞዋን ቀጠለች… ደብተሮቿን አቅፋ፣ ነጠቅ ነጠቅ እያለች…
ጥቂት እንደሄደች ግን፣ ከበስተኋላዋ የሆነ ድምጽ ተሰማት… የፈረስ ኮቴ ድምጽ… ጉዞዋን ሳታቋርጥ ዘወር ብላ ተመለከተች፡፡ ሰውዬው ፈረሱ ላይ ጉብ ብሎ ከራስጌዋ ተዘብቧል፡፡ ሌሎች በየጥሻው መሽገው የነበሩ ጓደኞቹም ከያሉበት ብቅ ብለው ዙሪያዋን ከበዋታል፡፡
ሰውዬው ልጓሙን ጨብጦ፣ አንዳች ጉጉት ፊቱ ላይ እየተንቀለቀለ፣ በጎመዠ አይን ቁልቁል እያያት ከኮርቻው ላይ ዘሎ ወረደ፡፡ አበራሽ በድንጋጤ ክው ብላ፣ ደብተሮቿን ጥላ በፍርሃት ተንቀጠቀጠች፡፡ በጭንቅ ተውጣ ተብረተበተች። የሆነ መጥፎ ነገር እየመጣባት ስለመሆኑ አልተጠራጠረችም፡፡ ከፈረሰኛው ሩጣ ለማምለጥ አቅም እንደሌላት የተረዳችው ጉብል፣ ባለችበት ቆማ ለጠለፋ ተዘጋጅተው የከበቧትን ወንዶች እያየች እሪታዋን አቀለጠችው፡፡
ጩኸቷን ሰምቶ የደረሰላት አልነበረም፡፡ ፈረሰኛው ልጅቷን አፈፍ አድርጎ አንስቶ ከኮርቻው ቀዳማይ ኋላ አስቀመጣት፡፡ እሷ በውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ እየቃተተች ስትወራጭ፣ እሱ በደስታ እየተፍለቀለቀ ፈረሱን ኮልኩሎ ሽምጥ ጋለበ፡፡ በለስ የቀናቸው ጓደኞቹ “ያሆ በል!...” በሚል የድል ዜማ አጅበው ሸኟቸው - ሰውዬውንና ጠልፎ ያገኛት ሚስቱን፡፡
ሰውየው ጨከነ፡፡
ቢወልድ የሚያደርሳትን ልጃገረድ፣ ያለርህራሄ ልብሷን ቦጫጭቆ እርቃኗን አስቀራት፡፡ ከጎኑ ባጋደመው ጠመንጃ አስፈራርቶ፣ አስገድዶ ደፈራት፡፡ እሷ በደም አበላ እየታጠበች ስትንሰቀሰቅ፣ እሱ ወንድነቱን አፍስሶባት እፎይ ብሎ ተነፈሰ፡፡ ወለል ላይ እንደተዘረረች ትቷት ተነሳ፡፡ ዘወር ብሎም አላያትም፡፡ ዘወር ቢል ኖሮ፣ የአበራሽ እጆች ሲንቀሳቀሱ ያይ ነበር፡፡ ከደቂቃዎች በፊት እሷን ሲያስፈራራበት የነበረውን የገዛ ጠመንጃውን ስታነሳ፣ አንስታም ወደ እሱ ስታነጣጥር፣ ቃታ ስባ ጥይት በእሱ ላይ ስትቆጥር ያይ ነበር፡፡
ድንገተኛ የተኩስ ድምጽ ተሰማ፡፡
ሰውዬው ወለል ላይ ወድቆ ደም ያጎርፋል፡፡ የቆሰለ አካሉን ይዞ እየተወራጨ ይቃትታል፡፡
አበራሽ በጠለፋትና አስገድዶ በደፈራት በዚህ ጨካኝ ሰው ላይ በተፈጸመው የግድያ ወንጀል ተጠርጥራ እስር ቤት ገባች፡፡ ዋስ ጠበቃ ሆኖ የሚቆምላት አልነበረም፡፡ የዋስ መብቷ ሳይከበርላት በለጋ እድሜ በእስር መማቀቅ ዕጣዋ ሆነ፡፡
ከጊዜያት በኋላ…
የህግ ባለሙያዋ መዓዛ አሸናፊ ስለ አበራሽ ሰማች፡፡ ጠልፎ የደፈራትን ወንድ በጠመንጃ ተኩሳ ገድላለች ተብላ ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ በእስር ቤት እየተሰቃየች ስላለችው አበራሽ መረጃ የደረሳት መዓዛ ጊዜ አላጠፋችም፡፡ ልጅቷን ተሟግታ ከስቃይ ነጻ ልታወጣት ተነሳች፡፡ እናም በስንትና ስንት ውጣውረድ ያሰበችው ሆነላት፡፡
አሁን …
ከአመታት በፊት ሰሚ አጥታ በእስር ቤት ስትሰቃይ የኖረችዋ ልጅ ታሪክ፣ በብዙዎች ተሰማ። ከዚያች የገጠር መንደር አልፎ ከተማ ደረሰ፡፡ አዲስ አበባን አልፎ ተሰራጨ፡፡ አሳዛኙ ታሪኳ አሁን ደግሞ፣ አሜሪካ ተሻግሮ ብዙዎችን ያነጋገረ አለማቀፍ ፊልም ሆነ፡፡
የአንጀሊና ጆሊንና የኢትዮጵያን ስም ዳግም አስተሳስራ ያስነሳችው አበራሽ ናት፡፡ መገናኛ ብዙሃን ባሳለፍነው ሳምንት እነዚህን ስሞች ደጋግመው ያነሱት፣ አንጀሊና ጆሊ በአበራሽ እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራውን “ድፍረት” የተሰኘ የአማርኛ ፊልም በሚገርም ሁኔታ በማድነቋ ብቻም አይደለም፡፡ አለማቀፍ ዝና ያላት የሆሊውዷ ፈርጥ አንጀሊና፣ የዚሁ ኢትዮጵያዊ ፊልም ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር የመሆኗ አስገራሚ እውነት እንጂ፡፡
በኢትዮጵያዊው የፊልም ባለሙያ ዘረሰናይ ብርሃነ መሃሪ የተሰራውና ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ፓርክ ሲቲ በተጀመረው ሰንዳንስ አለማቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ በ‘ወርልድ ሲኒማ ድራማቲክ ውድድር’ ዘርፍ በዕጩነት የቀረበው፣ “ድፍረት” የተሰኘ ፊቸር ፊልም በታዋቂዋ የሆሊውድ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰርነት መሰራቱንና ከፍተኛ አድናቆት ማግኘቱን ቀድሞ የዘገበው ኢንዲዋየር የተባለው ድረገጽ ነው፡፡
“ልብ የሚሰቅል ድንቅ ታሪክ፣በሚያምር የፈጠራ ክህሎት ተውቦ የቀረበበት ፊልም ነው። እንዲህ ያለ ፊልም መመልከት መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡ የኢትዮጵያን የባህል ብዝሃነት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ ባህላዊ ልማዶችን ሳይጋፉ የህግ የበላይነትን ማስከበር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነም ያመለክታል፡፡” ብላለች - አንጀሊና ጆሊ ስለፊልሙ ስትናገር፡፡
 የፊልሙ ታሪክ የኢትዮጵያን መጻኢ ዘመን ብሩህነት እንደሚያሳይ የገለጸችው አንጀሊና፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ልጃገረዶች በመሰል ሁኔታ ያለ ህግ ከለላ የሚያድጉባቸውን ሌሎች አገራትም ወደተሻለ አቅጣጫ እንዲጓዙ የሚያመላክት እንደሆነ  ተናግራለች፡፡ በፊልሙ ውስጥ ያለችውን የህግ ባለሙያ የመሳሰሉ ጀግና ሴቶች፣ አንድን ማህበረሰብ ለለውጥ እንዲነሳ የመቀስቀስ አቅም እንዳላቸው እንደሚያሳይም ገልጻለች፡፡
“የዚህ ፊልም መምጣት፣ በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ውስጥ እንደ ታላቅ ምዕራፍ የሚቆጠር ነው” ብላለች - አንጀሊና ጆሊ ስለ ፊልሙ ያላትን አድናቆት ስትገልጽ፡፡ አንጀሊና ጆሊ ለፊልሙ ያላትን አድናቆት በይፋ መግለጧ፣ የፊልሙን ተቀባይነት ከፍ እንደሚያደርገውና ምናልባትም ከፌስቲቫሉ በኋላ በአሜሪካ ለሽያጭ የሚበቃበትን ትልቅ ዕድል ሊፈጥርለት እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ ታዲያስ መጽሄት ከኒውዮርክ እንደዘገበው፣ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በኡታህ ፓርክሲቲ በተጀመረው ሰንዳንስ የፊልም ፌስቲቫል ላይ እንዲሳተፍ የተመረጠውና የድራማ ዘውግ ያለው ፊልሙ፣ ካለፈው እሁድ ጀምሮ በኢጂብሽያን ቲያትር፣ በብሮድዌይ ሴንተር ሲኒማ፣ በላይብረሪ ሴንተር ቲያትርና በሆሊዴይ ቪሌጅ ሲኒማ ለተመልካች እየቀረበ ይገኛል፡፡
የ“ድፍረት” ደራሲና ዳይሬክተር ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ዘረሰናይ ብርሃነ መሃሪ ሲሆን ከአሜሪካ ዩኤስሲ ስኩል ኦፍ ሲኒማቲክ አርትስ በፊልም የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። በፊልም ስራ ከአስር አመት በላይ ልምድ ያካበተው ዘረሰናይ፣ ሃይሌ አዲስ ፒክቸርስ የተባለ የፊልም ኩባንያ በማቋቋም ነው ይሄን “ድፍረት” የተሰኘ የመጀመሪያ ሥራውን ለእይታ ያበቃው፡፡  
ታዋቂዋ የሆሊውድ ተዋናይ አንጀሊና ጆሊ፣ ከአምስቱ የፊልሙ ኤክስክዩቲቭ ፕሮዲዩሰሮች አንዷ መሆኗ ታላላቅ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ ሲሆን ለፊልሙ ስኬታማነትም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት እየተገለፀ ነው። ከአንጀሊና በተጨማሪ ጁሊ ምህረቱ፣ ጄሲካ ራንኪን፣ ፍራንሴስካ ዛምፒ እና ሌሲ ሽዋርዝም የፊልሙ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰሮች እንደሆኑ ታውቋል፡፡  የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር የሆነው ዘረሰናይ፣ ከኢትዮጵያውያኑ ምህረት ማንደፍሮና ሊላይ ደመወዝ ጋር የፊልሙ ፕሮዲዩሰር ነው፡፡
የታሪኩን ባለቤት አበራሽን በቀለን ሆና የተወነችውን ታዳጊ ትዝታ ሃገሬንና የአበራሽ ጠበቃ መዓዛ አሸናፊን በመሆን የተጫወተችውን  ሜሮን ጌትነትን ጨምሮ ከ371 በላይ አንጋፋና ወጣት ተዋንያን የተሳተፉበት “ድፍረት”፣ ቀረጻው በኢትዮጵያ እንደተከናወነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፊልሙ ስራ ላይ ከተሳተፉት ባለሙያዎች ግማሽ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውም በፊልሙ ፕሮጀክት ድረገጽ ላይ የወጣው መረጃ ይገልጻል። በሰንዳንስ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የቀረበ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፊልም እንደሆነ የተነገረለት የዘጠና ዘጠኝ ደቂቃ እርዝማኔ ያለው ፊልሙ፣በአማርኛ ቋንቋ የተሰራና የእንግሊዝኛ መግለጫ (ሰብታይትል) ያለው ነው፡፡  
የፊልሙ ሲኒማቶግራፈር ሞኒካ ሌንዜውስካ ስትሆን አጄንስካ ግሊንስካም በኢዲተርነት ሰርታለች፡፡ የፕሮዳክሽን ዲዛይነርነቱን ስራ፣ ዳዊት ሻዎል ሲያከናውነው፣ የፊልሙን ማጀቢያ ሙዚቃ የሰሩት ደግሞ ዴቪድ ሾመርና ዴቪድ ኤጋር የተባሉ ታዋቂ የሙዚቃ ባለሙያዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ኢንዲዋየር  ፊልሙን በተመለከተ ባወጣው መረጃ መሰረት፣ የአበራሽ ጠበቃ የነበረችዋን መዓዛ አሸናፊን ወክላ በፊልሙ ላይ የተጫወተችው ተዋናይት ሜሮን ጌትነት፣ በፌስቲቫሉ ላይ እንዲሳተፉ ከተመረጡ የፊልሙ  አስር ተዋንያን መካከል አንዷ በመሆን ወደ አሜሪካ አቅንታለች፡፡

Published in ጥበብ
Monday, 27 January 2014 08:32

ሞትና ዚቅ

የመቃብር ላይ ጽሑፎች - 1
በድንጋይ ላይ የተቀረፁ
ፓት ስቲል እዚህ አርፏል፡፡ ይህ እውነት ነው። ማን ነበረ! ምን ነበረ! ምን ይፈይዳል? በቃ እሱ እዚህ አርፏል፡፡ ምክንያቱም ስለሞተ፡፡ ሌላ አዲስ ነገር የለም፡፡
የመቃብር ሀውልቴ ፊት ለፊት ቆማችሁ ይህን ጽሑፍ ለምታነቡ ሁሉ! ጨካኙ ሞት እኔን በቁጥጥሩ ስር እንዳዋለኝ፤ሁልሽንም ያንበረክክሻል፡፡ ይልቅስ ጊዜ ሳታጠፉ ንስሀ ግቡ፤ ክርስቶስ ለፍርድ ተመልሶ ሳይመጣ፡፡ ህይወት የማለዳ ጤዛ ናትና፡፡
እዚህ ያረፈው ቶማስ ኬምፕ ነው፡፡ ውድ ውድ ሱፎችን እያማረጠ ሲዘንጥ እንዳልኖረ፤ በአቡጄዲ ጨርቅ ተጠቅልሎ ፡፡
ማርጎሪ ሚኮል፤ አንድ ጊዜ ኖረ! ሁለቴ ተቀበረ!

ቤተሰቦች
እህትማማቾቹ በ24 እና 22 አመት እድሜያቸው በድንገተኛ አደጋ ተቀጠፉ፡፡ በህይወት ዘመናቸው ትሁትና እርስ በርሳቸው እጅግ የሚፋቀሩ ነበሩ፡፡ በሞታቸውም አልተለያዩም፡፡
ጆን ክሪተን፤ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ በተቀበሩበት በዚህ ስፍራ አርፏል፡፡ ሞት የሁላችንም  ዕጣ ፈንታ መሆኑን መቸም አትዘነጉትም፡፡ ከዚያ በፊት ግን  አንድ ትልቅ እድል እጃችሁ ላይ አለ - መንግስተ ሰማያት ለመግባት መፀለይ፡፡

ጥንዶች
ፍቅርና እድሜ ተሰናስለው በዚህ ድንጋይ ስር እፎይ ብለዋል፡፡ ጥንዶቹ፤ በዚህ የሞት እልፍኝ ውስጥም፤ አካላቸው ፈራርሶ እፍኝ አፈር እስኪሆኑ መቆራኘት ምርጫቸው ሆኗል፡፡ በፍቅር ከፍ አድርገው የሚያነሱት ቲም ብሎ የሞላ ዋንጫቸው፤ ፈራርሰው ከመበስበስ ይታደጋቸው ዘንድ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡
አደንና አሣ ማጥመድ ያዘወትሩ በነበሩ ጥንዶች ሀውልት አናት ላይ፤ የቀበሮና የአሣ ቅርፆች ታትመዋል፡፡ ከስሞቻቸው ስር፤ በመቃብር ስፍራቸው በኩል ለሚያልፉና ዞር ብለው ለሚያስተውሉ ሁሉ አንድ የተማፅኖ ጽሑፍ በጉልህ ይታያል… የአንድ ደቂቃ ጸሎት?

ለባሎች
ውድ ባሌ በዚህ ስፍራ አረፈ፡፡ የጎጇችን ፀዳል ጨለመ፡፡ ያ የምንወደውና ለመስማት የምንናፍቀው ድምፁ ፀጥ  እረጭ አለ፡፡ በቤታችን ውስጥ እሱን በስስት የምናይበት፣ ዘወትር የሚቀመጥበት ቦታ አሁን ባዶ ነው፡፡ በምንም የማይሞላ - ኦና!
ወደር የለሽና ዕፁብ ድንቅ ባህሪ ነበረው። እናንት እንግዶች፤በእርግጥ አታውቁት ይሆናል፤ይኸው ዛሬ ተዋወቁት፤እናም ለዚህ ንፁህና ታማኝ ሰው እንባችሁ ይፈስስ ዘንድ አትከልክሉት!

ለሚስቶች
ውድ ባለቤቴ፤ ስለ እኔ ማቅ አትልበስ፤አንዴ ሞቼ እርቄያለሁና፡፡ ፍቅሬ፤ ይልቅስ ከእግዚአብሔር ጋር ልጆቼን ተንከባከብልኝ፤አደራ! ስለ እኔ ስለምትወዳት እናታቸው ብለህ፡፡
አምርሬ የማለቅሰው፤ ካንቺ ጋር የኖርኩትን ዘመን በግብዝነት፣ በከንቱ ስለማሳለፌ ነው። ብቻዬን ጥለሽኝ ከሄድሽ ወዲህ በረሀ ላይ መውደቄን ሳይ፤ የህይወቴ ልምላሜ ምንጭ አንቺ እንደነበርሽ ከረፈደ ቢገባኝ፡፡
የኔ ውድ ባል፤ እነሆ የህይወት ዘመኔ ተፈፀመ፤ላንተ ያለኝ ፍቅር ግን በሞትም አይነጥፍም።

የኃይማኖት ሰዎች
ለሃምሣ አመታት ያህል፤ እስከ የጳጳስነት የማዕረግ አጣብቂኝ ድረስ ሀገሬን አገልግያለሁ፡፡ በግፍ የሚተላለቁ ልዑላንንም በተፋፋመ ጦርነት መሀል ባርኬያለሁ፡፡
በእርግጥ በእነዚያ ወቅቶች፤ በእነዚያ ስፍራ የቆምኩትም ሆነ የአስከፊ ጦርነቶቹ ሁሉ መነሾ መዘዙ እኔ አልነበርኩም፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው፤በሁለቱም ጉዳዮች አለመገኘትም ደግሞ አልቻልኩም፡፡ ባልጎድፍም፤ ጠርቼ አልጠራሁም።
በውስጧ እንደታቀፈቻቸው ከንቱ ነገሮች ሁሉ፤ ዓለም ቀልድ መሆኗን ደጋግሜ አስቤ አውቃለሁ፡፡ አሁን ግን በደንብ አረጋግጫለሁ፡፡

ክቡር እምክቡራኑ
ህይወቱን ሙሉ ተንቀባርሮ በድሎት ኖሯል። 57 አመት ሲሆነው ግን ወደ ሚቀጥለው ህይወት ለማለፍ ወደደ፡፡
እንግዲህ ለምቾቱ ከምድር የሰማዩን የገነት አካባቢ ቢመርጥ ነው እንጂ…አንዳችም ሳይጎድልበት?ሆ! ለማንኛውም፤ በዚህ ስፍራ እግር የጣላችሁ እስቲ ፀልዩለት፤ወደ መንግስተ ሰማይ መግቢያ መስፈርቱን ቢያሟላለት፡፡ መግባቱ ባይቀርም፡፡
ሽክ! ብሎ ሲወጣ ሲገባ፤ገና ለገና ለምን አማረበት ብሎ በቅናት የተንጨረጨረበት ጮሌው ሞት ከመሀከላችን ነጥቆ ወሰደው፡፡ ብቻ ይኼ የጊዜ ስስታም ነዝናዛ ፤ ልዑሉን እዚያም ከወሰደው በኋላ በሆነ ባልሆነው እያመካኘ እንዳይነተርከው ነው ስጋታችን፡፡ ሲፈጥረው ጭንቅ አይችልማ፤ መስፍናችን!

መርከበኞች
እ.ኤ.አ በ1870 ድንገተኛው የሀሪኬን ማዕበል ተከስቶ፤ ወደ ዌስት ኢንዲስ በመጓዝ ላይ የነበረውን የአየርላንድ ንጉሥ የግል መርከብ የባርባዶስ ተጓዦችና የመርከቡ ሠራተኞች ሁሉ ሲያልቁ፤ አብሮ ለሞተው ወላጅ አባቱና በሀዘን ተቆራምዳ ስትብሰለሰል ሰንብታ ከሦስት አመታት በኋላ ባሏን ለተከተለችው ምስኪን እናቱ፤ካፒቴኑ ልጃቸው ለመታሰቢያ ባቆመላቸው ሀውልት ላይ የሰፈረ…
ኦ! አንት ብርቱ የውቅያኖስ ማዕበል
እሱን አቅሉን አናግተህ አላግተህ የዋጥክ፤
ውለህ አድረህ እሷንም ወሰድካት
በፍቅሩ የናፍቆት ማዕበል፣ እያርገፈገፍክ ክፉኛ እየናጥክ!
ምናምኒት የበሽታ ዘር የሚባል ሽውም ሳይልብኝ፤ እንደው ‹‹ምች››ንኳ ሳያገኘኝ፤ ገና በለጋ ወጣትነቴ ነው የተቀጨሁት፡፡
ሰላማዊ ሆኜ ኖሬ ፤ በሰላማዊ ሁኔታ፤ ጤነኛ ሳለሁ ተቀበርኩ፡፡ የዘወትር ፀሎቴ ረዥም ዕድሜን ለመኖር ቢሆንም፤ እግዜሩ እምቢ አለና፤ እነሆ እንዳርፍ ተገደድኩ፡፡ እንጃ ሳላውቅ ምን እንደፈፀምኩ፡፡
ማዕበልና ሞገድ ወዲያ ወዲህ እያንገላታኝ ስንከራተት ኖሬ፤ በመጨረሻ ከዚህ ስፍራ መልህቄን ጣልሁ ፤ የህይወት ጉዞዬ መዳረሻ፣ ማረፊያ ወደብ ሆነኝ መቃብሬ፡፡ እንግዲህ  ከአፈሩ ቤቴ፤  እስከ ፍርዱ ቀን በሰላም አርፎ አጥንቴ፤ ለትንሣኤው እበቃ ዘንድ፤ ለዘለዓለሙ የፅድቅ እርስቴ፤ ወገኖቼ፤ እንደምትፀዩልኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በማይናወጥ ፅኑ እምነቴ፡፡
ምንጭ - DEAD FUNNY.

Published in ጥበብ
Monday, 27 January 2014 08:30

ፖም - ጥቅምና ጥንቃቄው

የፖም ጭማቂዎች ፓስቸራይዝድ መሆናቸውን አረጋግጡ
የመርሳት በሽታን (አልዛሂመር) ይከላከላል
ፖም የሚመገቡ ሰዎች ሸንቃጣ ናቸው  

አትክልትና ፍራፍሬ አዘውትሮ መመገብ ከፍተኛ የጤና ጥቅም እንዳለው ተመራማሪዎች ይናገራሉ፤ ይመክራሉ፡፡ የእኔም አነሳስ ይህንኑ ሐሳብ የሚያጠናክር ነው - አመጋገብን በማስተካከል ማለትም አትክልትና ፍራፍሬ በብዛት፣ ፕሮቲንና ካርቦሃይድሬት በመጠኑ በመመገብ ጤናማ ሕይወት ይምሩ የሚል፡፡
አንዲት ልጅ አውቃለሁ፡፡ - “ሀበሻና ቢላዋ የሰባ ይወዳል” የሚለውን አባባል የምትደግፍ ናት፡፡ በሳምንት አንድ ጊዜ፣ ከተመቻቸላት ሁለትና ሦስት ጊዜ ጥሬ ሥጋ ትበላለች፤ ቢጠፋ ቢጠፋ በ15 ቀን አንዴ ሳትበላ አትቀርም፡፡ የዚህቹ ልጅ የጨው አጠቃቀም የሚገርም ነው፡፡
ምግብ ውስጥ ለሌላ ሰው “ኖርማል” የሆነው የጨው መጠን፣ እሷ ጋ ሲደርስ ባዶ ይሆንባታል። ስለዚህ ጨው ነስንሳ ነው የምትበላው፡፡ ስኳርም እንደዚያው ነው፡፡ እሷን ባየሁ ቁጥር ከበርካታ ዓመታት በፊት ብሪቲሽ ካውንስል ላይብረሪ ያነበብኩት Women’s weekly የተባለ መጽሔት ትዝ ይለኛል፡፡
መጽሔቱ፣ “መርዝ እንደምትፈሩ ሦስቱን ነጮች (ጨው፣ ስኳር፣ ጮማ) ፍሩ” ይላል። ታዲያ፤ እነዚህን የጤና ጠንቅ የሆኑትን ምግቦች የምትወደው እሷ ብቻ አይደለችም፣ ብዙ ሰዎች እነዚህን ምግቦች ይወዳሉ፡፡ ይህ ጉዳይ፣ በሌሎች ጥናቶችም ስለተረጋገጠ አደጋ አለው!
የዛሬው ትኩረቴ፣ የፍራፍሬ ወገን በሆነው ቱፋህ ፖም ወይም አፕል የሕክምና ጥቅምና ጥንቃቄ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ፖም፣ ከፍተኛ የጤና ጥቅም እንዳለው ብዙ ጊዜ ሰምታችኋል ብዬ እገምታለሁ። እኔም የምለው ይኼው ነው፡፡ ነገር ግን በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ብናምንም፣ “ጠርጥር፣ ከገንፎ ውስጥ ይገኛል ስንጥር” እንደሚባለው ጥንቃቄም ማድረግ እንዳለብን ማወቅ ይገባናል፡፡

የፖም ጥቅም
አልዛሂመርን ይዋጋል - ይህ፤ በዕድሜ የገፉ ሰዎች በሕይወታቸው ሙሉ የሚያውቁትን ነገር እንዲረሱ የሚያደርግ የአንጐል በሽታ ነው፡፡ በሽታው የያዛቸው ሰዎች፣ ከጥቂት ደቂቃ በፊት ያደረጉትን ነገር እንዲሁም እናታቸውን ጭምር ሊዘነጉ ይችላሉ።
ፖም፣ የአንጐል ሴሎች እንዳያረጁ የሚያደርግ ከርሰቲን (quercetin) የተባለ ኃይለኛ ፀረ - ኦክሲደንት (ኦክሲጅን ከሌላ ንጥረ - ነገር ጋር ሲዋሃድ የሚፈጠር ቅሪት ወይም ዝቃጭ) ኬሚካል አለው፡፡
ይህ ኬሚካል፣ በአይጦች ላይ ተሞክሮ ጥሩ ውጤት ስላስገኘ፣ ሳይንቲስቶች ለሰው ልጅም ሳይጠቅም አይቀርም የሚል እምነት አላቸው፡፡
የቱፋህ ቆዳ መመገብ ብዙ በሽታ ተዋጊ ውህድ ያስገኛል ብሏል Reader’s digest USA በኦክቶበር 2013 እትሙ፡፡ ስለዚህ ለምግብነት ትናንሽ ፖሞችን ይምረጡ፡፡ ምክንያቱም ትላልቆቹ ፈጥነው ስለሚበስሉ የጤና ጥቅማቸው እያበቃ ሊሆን ይችላል፡፡
የደንዳኔ (colon) ካንሰር ይከላከላል - በቅርቡ በጀርመን የተደረገ አንድ ጥናት፤ ተፈጥሯዊው የፖም አሰር (Fiber) በደንዳኔ ውስጥ ሲብላላ ወይም ፈርመንት ሲያደርግ የካንሰር ሴሎች እንዳይፈጠሩ የሚያደርጉ ኬሚካሎች እንደሚፈጠሩ አመልክቷል።
ሌሎች ጥናቶች ደግሞ በፖም ውስጥ የሚገኘው ፕሮካአዲያን (Procyanidins) የተባለ ፀረ ኦክሲደንት፣ የካንሰር ሴሎችን የሚገድሉ በርከት ያሉ ሴሎች እንዲነቃቁ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የደም ስኳር እንዳይዋዥቅ ያደርጋል - ፖም፤ በሟሚ አሰር የተሞላ በመሆኑ፤ የምግብ ስልቀጣና ጉሉኮስ ከደም ጋር የሚቀላቀልበትን ፍጥነት ያዘገያል።
አንድ የተመራማሪዎች ቡድን፣ በቀን ቢያንስ አንድ ፖም የሚበሉ ሴቶች ከማይበሉት ጋር ሲነፃፀር፤ በስኳር ሕመም የመያዝ ስጋታቸው 28 በመቶ መቀነሱን ደርሶበታል፡፡
የድድን ጤና ከፍ ያደርጋል - ፖም ተፈጥሯዊ የጥርስ ማጽጃ መሆኑ ከታወቀ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ፖም መብላት ጥርስ ማጽዳት ባይሆንም፤ ፖም ገምጦ ማኘክ ድድ እንዲነቃቃ ያደርጋል፡፡
ጣፋጭነቱ ደግሞ የምራቅ ምርት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ይህ ሁኔታም፣ በአፍ ውስጥ የሚኖሩትን ባክቴሪያዎች መጠን ዝቅ በማድረግ፣ የጥርስ መበስበስ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊትን ይከላከላል - በቅርቡ በተደረገ ጥናት መሠረት፣ ፖም የተመገቡ አዋቂ ሰዎች በደም ግፊት የመያዝ ዕጣቸው 37 በመቶ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ ሸንቃጣ ያደርጋል - ፖም በፋይበርና በውሃ የተሞላ ነው፡፡ ፖም ከበሉ፣ ሆድ ለመጥገብ የሚፈልገው አነስተኛ ምግብ ስለሆነ ብዙ አይመገቡም፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በቀን ቢያንስ ሦስት ፖምና (ሥዕላዊ መዝገበ ቃላት ሸክኒት ይለዋል - ሞለል ያለ አረንጔዴ ወይም ቢጫ የሆነ ውስጡ ነጭ ጣፋጭ ፍሬ) የሚበሉ ሰዎች፣ ክብደት እንደሚቀንሱ ከዋሽንግተን ስቴትና ከብራዚል የወጡ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡
ከፍተኛ ኮሌስትሮልን ይዋጋል - የፖም ካሎሪ (ኃይል ሰጪነት) ዝቅተኛ ሲሆን ፐክቲን (Pectin) የተባለው ሟሚ አሰር (Fiber) መጠን ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ሁኔታም፣ የደም ስሮችን (አርተሪስ) የሚጐዳውን ኤል ዲኤል (LDL)  የተባለ የደም ኮሌስትሮል መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡

ፖም ያለው የጤና ስጋት
ፀረ - ነፍሳት መድሃኒት - ፖም፤ ለትላትሎች፣ ቆዳውን ለሚጐዱና Scale ለተባሉ የተለያዩ ነፍሳት የተጋለጠ ነው፡፡ ይሄን ለመከላከል በርካታ የፖም ዝርያዎች ፀረ - ነፍሳት መድሃኒት ይረጭባቸዋል። ስለዚህ ፖም ከመግመጥዎ በፊት ይጠቡት፡፡ እንዲሁም፤ የሚረጨው ፀረ - ነፍሳት ወደ ውስጥ እንዳይገባ፣ ፖሙ ሰም ተቀብቶ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሰም የተቀባ ፖም ካጋጠምዎት፣ ቆዳውን ልጠው ይመገቡ፡፡
አለርጂ - የደረቀ ፖም፤ እርጥበቱንና ቀለሙን እንደያዘ እንዲቆይ፣ ብዙ ጊዜ ሰልፈርዳይኦክሳይድ ይጨመርበታል፡፡ ይሄ ደግሞ አለርጂ ያለባቸውን ሰዎች ሊቀሰቅስባቸው ስለሚችል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
የባክቴሪያ ኢንፌክሽን - ሕፃናት፣ እርጉዝ ሴቶች፣ በዕድሜ የገፉና የበሽታ መከላከል አቅማቸው ደካማ የሆነ ሰዎች ፓስቸራይዝድ ያልሆነ የታሸገ የፖምና የሲደር (cider) ጭማቂ ሲጠጡ ኢ.ኮሊ (E.cole) እና ክሪፕቶስፓርዲየም (Cryptosporidium) የተባሉት ባክቴሪያዎች፣ ለአደገኛ በሽታ ያጋልጣሉ።
ስለዚህ የተጠቀሱት ሰዎች የታሸገ የፖምና የሲደር ጭማቂ ከማግዛታችን ወይም ከመጠጣታችን በፊት ፓኮው ላይ ፓስቸራይዝድ መደረጋቸውን ማረጋገጥ አለብን፡፡

Published in ዋናው ጤና

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን ቁጥራቸው እየበረከተ የመጡት ቀያይ ሲኖትራክ ከባድ መኪናዎች በመንገደኞች ላይ አሰቃቂ አደጋ እያደረሱ ሲሆን ነዋሪዎችም “ቀይ ሽብር” የሚል ቅጽል ስም እንደሰጧቸው ይናገራሉ፡፡

ኮልፌ አካባቢ በ350 ብር ቤት ተከራይታ የምትኖረው የ31 ዓመቷ ማህሌት አሸናፊ፤ በወሲብ ንግድ ነበር የምትተዳደረው፡፡ ቀን ቀን የሁለት ዓመት ልጇን ስትንከባከብ ትውልና ምሽት ላይ ልጇን ለሞግዚት  ሰጥታ “ቢዝነስ”  ትወጣለች። ማህሌት ቦሌ ሩዋንዳ ከሚኖሩት ወላጆቿ ጋር የተለያየችው በእርግዝናዋ ሳቢያ ነው፡፡ ዘወትር “ቤተሰቤን ያጣሁበት ነው” ለምትለው ልጇ ያላት ፍቅር ልዩ ነው፡፡ ማታ ማታ ለ”ቢዝነስ” ስትወጣ እንኳን እንደሌሎች ባልደረቦቿ  አታድርም፡፡ ቢዝነስ ቀናትም አልቀናትም ቢበዛ እስከ ሰባት ሰዓት አምሽታ ልጇ ጋ ትመለሳለች፡፡
ዘንድሮ አዲስ ዓመት ላይ ከወሲብ ንግድ ወጥታ ሌላ ስራ ለመቀጠር የወሰነችውም ለልጇ በማሰብ ነው - “እያደገ ሲመጣ ስሜቱ ይጎዳል” በሚል፡፡ እናም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፈሯ በሚገኝ ካፌ ውስጥ ተቀጥራ መስራት ጀመረች፡፡ ለረዥም ጊዜ አይታቸው ከማታውቀው እናቷ መልዕክት የደረሳትም ይሄኔ ነው፡፡ በጠና መታመማቸውንና ዓይኗን ለማየት እንደጓጉ ሰማች፡፡ የእናትን አንጀት ታውቀዋለችና አላስቻላትም፡፡  ወደ እናቷ ቤት ለመሄድ ተነሳች፡፡ ግን ፍርሃት ፍርሃት ብሏት ነበር፡፡ “ልቤ ፈራ---እናቴ ሞታ እንዳይሆን…” ስትል ስጋቷን ለልጇ ሞግዚት አካፍላታለች፡፡ ከቤት ከመውጣቷ በፊት ልጇን አገላብጣ ሳመችው - ሩቅ አገር እንደሚሄድ ሰው፡፡ ምናልባት እናቷ አርፈው ከሆነ ማደርም ሊኖር ይችላል ብላ ያሰበችው ማህሌት ካፌ ለምትሰራ ጓደኛዋ ልጇን እንድታይለት አደራ ስትላት ለምን ይዘሽው አትሄጅም የሚል ሃሳብ አቅርባላት ነበር፡፡ ማህሌት ግን “ምናልባት ችግር ካለ በእኔ ብቻ ይለፍ” አለችና ወደ እናቷ ቤት ለመሄድ ጉዞ ጀመረች፡፡
በተለምዶ 18 ማዞሪያ በሚባለው አካባቢ መንገድ ለመሻገር ቆማ ሳለ፣ ከጦር ሃይሎች አቅጣጫ  የመጣ  አንድ ሲኖትራክ  መንገድ ይስትና ማህሌትንና ሌሎች ሦስት መንገደኞችን ይገጫል፡፡ እሷ ወዲያው ህይወቷ ያለፈ ሲሆን የቀሩት ከባድና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው የፖሊስ መረጃ ያመለክታል፡፡
የ26 ዓመቱ ወጣት ቴዎድሮስ አበራ፤ የ4ኛ አመት ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነበር፡፡ ለቤተሰቡ ብቸኛ ልጅ ስለሆነ ወላጆቹ እንደ አይናቸው ብሌን ነው የሚያዩት፡፡ ባለፈው ህዳር አንድ ጠዋት ላይ ነው፡፡ ከዩኒቨርስቲ ጓደኞቹ ጋር የጥናት ቀጠሮ ቢኖረውም መጀመርያ የታመሙትን እናቱን ወይዘሮ እቴነሽ ሳህሉን ወደ ሆስፒታል መውሰድ ነበረበት፡፡ ሳሪስ አዲሱ ሰፈር ከሚገኘው መኖርያ ቤታቸው እናቱን በሃች ባክ መኪና ይዞ ወጣ፡፡ ስለመንገዱ መጨናነቅ ለእናቱ እያወራ ነበር የሚያሽከረክረው፡፡ ዘንባባ ሆስፒታል መታጠፊያ ጋር ሲደርሱ ከፊት ለፊት የሚመጣው ሲኖትራክ ያላማራቸው እናት፤ ልጃቸው ጥግ እንዲይዝ ይነግሩታል፡፡ ጥግ ከመያዙ በፊት ግን ያለአቅጣጫው እየተክለፈለፈ የመጣው ከባድ መኪና፣ ሃች ባክዋን በሹፌሩ በኩል ክፉኛ ገጭቶ ከመንገዱ ውጭ ወረወራት፡፡
የቴዎድሮስ እናት ወ/ሮ እቴነሽ ሳህሉ፤ ሆስፒታል ከገቡ ከረዥም ሰዓት በኋላ ነበር ራሳቸውን ያወቁት።  ሲነቁ  አንድ እግራቸው ከጥቅም ውጭ ሆኗል። ወዲያው ስለልጃቸው መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ማንም እውነቱን ለመንገር አልደፈረም - በድንጋጤ አንድ ነገር እንዳይሆኑ በመፍራት፡፡
አደጋው በደረሰ በአስረኛው ቀን እናት ልጃቸው መሞቱን ተረዱ፡፡ በድንጋጤ ዳግም ራሳቸውን ስተው ለተጨማሪ አስር ቀን እዚያው ሆስፒታል ውስጥ ተኙ፡፡ አሁንም ስለአደጋው ሲያስታውሱ ስቅስቅ ብለው የሚያለቅሱት ወ/ሮ እቴነሽ፤ “ምናለ እኔን ወስዶ ልጄን ቢያተርፍልኝ” እያሉ በቁጭት ይቆዝማሉ፡፡
ህዳር 18 ቀን 2006 ዓ.ም ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት ገደማ ነው፡፡ ሃይሉ አበራና ቴዎድሮስ አበራ የተባሉ ወጣት የጐዳና ተዳዳሪዎች፣ የዘወትር ማረፍያቸው በሆነውና ፒያሳ በሚገኘው ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ደጃፍ ላይ ጐናቸውን አሳርፈዋል፡፡ አቶ አበራ ተሰማ እና አቶ ሞላ አበራ ደግሞ ቤታቸው እዚያው አካባቢ ሲሆን  ወደ ስራ ሲሄዱ “ሰላም አውለኝ” ለማለት ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ጎራ ይላሉ፡፡
ውጭ ደጃፉ ላይ እንደቆሙም አንድ ሲኖትራክ ከየት መጣ ሳይባል መንገድ ስቶ አራቱንም ይገጫቸዋል፡፡ ከፖሊስ በተገኘው መረጃ መሰረት፤ ሁለቱ የጎዳና ተዳዳሪዎችና አቶ አበራ ተሰማ ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ፣አቶ ሞላ አበራ የተባሉት ግለሰብ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በህይወት ተርፈዋል፡፡
የካቲት 1 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት ገደማ፣ በቦሌ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው በሻሌ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት አካባቢ አንዲት ባጃጅ፣ ሹፌሩን ጨምሮ ስድስት ሰዎችን ጭና እየተጓዘች ነበር - ዚያዳ አስፋው፣ ብሩክ ሲሳይ፣ ገብርኤላ ሙሉጌታ፣ ክርስቲያን ክፍሉ፤ መንግስቱ ጫፎ እና የባጃጁ ሹፌር። ባጃጇ ከሰሚት ተነስታ ፊጋ ተብሎ ወደጠራው ሰፈር እየተጓዘች ነበር፡፡ የባጃጁ ሹፌር “”ዛሬ ቀኑ ይከብዳል አይደል?” በማለት ባነሳው ወግ መነሻነት ጨዋታው ደርቶ ነበር፡፡ ድንገት ከተቃራኒ አቅጣጫ የመጣው ሲኖትራክ ግን እነሱንም ጨዋታቸውንም በታተናቸው፡፡ በአደጋው ሶስት ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ፣ በሶስቱ ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ ገልጿል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን ቁጥራቸው እየበረከተ የመጡት ቀያይ ሲኖትራክ ከባድ መኪናዎች በመንገደኞች ላይ አሰቃቂ አደጋ እያደረሱ ሲሆን ነዋሪዎችም “ቀይ ሽብር” የሚል ቅጽል ስም እንደሰጧቸው ይናገራሉ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ ምርመራ ቡድን መሪ፣ ረዳት ሳጅን ቶሎሳ፤ ሲኖትራኮች ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ በየወሩ ከስድስት እስከ ስምንት አደጋዎች እያደረሱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ረዳት ሳጅኑ ለአደጋው መብዛት እንደምክንያት ከጠቀሷቸው መካከል፤ የሹፌሮች ብቃት ማነስ፣ የተሽከርካሪዎቹ ፍሬን ቶሎ መሞቅ፣ ከተፈቀደላቸው ክብደት በላይ መጫንና በሃሰተኛ መንጃ ፍቃድ ማሽከርከር ይገኙባቸዋል። ሲኖትራኮች የተፈቀደላቸው የጭነት መጠን 132 ኩንታል እንደሆነ የሚናገሩት ረዳት ሳጅኑ፤ አብዛኛዎቹ ግን  ከሁለት መቶ በላይ ኩንታል እየጫኑ መንቀሳቀሳቸው ለአደጋው መባባስ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል - ረዳት ሳጅን ቶሎሳ። አንዳንድ የሲኖትራክ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው፤ የመኪኖቹ ጥራት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ይናገራሉ። ሲኖትራክ የቻይና ስሪት እንደሆኑ የጠቀሱት ረዳት ሳጅን ቶሎሳ፤ የመኪኖቹን የጥራት ደረጃና አጠቃላይ ይዞታ በተመለከተ ከአስመጪዎቹ ጋር በቅርቡ ውይይት እንደሚካሄድ ተናግረዋል። ሲኖትራክ የተባሉት ከባድ መኪኖች በአብዛኛው ቻይናዎች በተሰማሩባቸው የመንገድና የባቡር ሃዲድ ፕሮጀክቶች ላይ እያገለገሉ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡  

Published in ህብረተሰብ

ከሰው ቤት ተገኝቶ ምንድነው ቅልውጡ፣
ግብፆች ለሀበሻ ደግሰው ላይሰጡ፡፡
ይህ ቅኔ የተነገረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በግብጽ ቤተክርስቲያን ሥር በምትመራበትና፣ ዻዻሳት ከግብጽ ታስመጣ በነበረበት ዘመን ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው የሃይማኖት አባት እንይሾሙ የተጣለባቸው ገደብ ትክክል አይደለም፣ በሚል ውሣኔው ይሻርና ይታረም ዘንድ ጥያቄ ላነሱ ኢትዮጵያዊን ክብር ይግባቸው፡፡ ከሰላሣ ዓመት በላይ የወሰደው ሙግትና ድርድር ለፍሬ በቅቶ ኢትዮጵያዊያን ከራሳቸው የሃይማኖት አባቶቻቸውን ለመሾም በቁ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከ1600 ዓመታት በኋላ ለእኩልነትና ለነጻነት በቃች፡፡ አገሪቱ ለዚህ ማዕረግ እንድትበቃ ላደረጉት ለንጉሱ አጼ ኃይለ ስላሴና ረዳቶቻቸው ነፍስ ይማር ልባዊ ጸሎቴ ነው፡፡
እስከማውቀው ድረስ እስልምና እንደ ካቶሊኮችና ኦርቶዶክሶች አንድ ማዕከል የለውም። ይህ በመሆኑም ወደ ግብጽና ወደ ሌሎች አገራት ተጉዘው ተምረው  የመጡ  ሙስሊም ወንድሞቻችን የግብጽን ወይም የሌላ አገር ተጽዕኖ አላመጡምና  እድለኞች ነን፡፡
ከግብጽ ተጽዕኖ ነጻ የመውጣት ሁለተኛው የትግል ምዕራፍ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ግብፆች “በአባይ ወንዝ ላይ ምንም አይነት ኘሮግራም ይኑራችሁ መጀመሪያ የእኛን ፈቃድ ወይም ይሁንታ ማግኘት አለባችሁ፣ ይህን ታደርጉ ዘንድም አስገዳጅ አለም አቀፍ ስምምነት አለ፡፡ ለአባይ ወንዝ ታሪካዊ ባለመብቶች ነን” ይሉናል፡፡ ኢትዮጵያ የምታውቀው፣ የፈረመችውና የሚያስገድዳት ውል ባለመኖሩ የግብጽ ይሁንታ አትፈልግም በማለት የሕዳሴውን ግድብ በራሷ ጊዜ ጀምራለች፡፡ ይሄንንም በተግባር እንዲገነዘቡት አድርጋለች፡፡
አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፤ የሕዳሴውን ግድብ የመሠረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ጊዜ፣ “ግድቡ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ግብጽንም፣ሱዳንንም ስለሚጠቅም መሠራት የነበረበት በሶስቱም አገሮች ገንዘብ ነበር” የሚል መንፈስ ያለው ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ግብፆች የግድቡን ትክክለኛ ባህሪ ከመረዳት ይልቅ እንደ አንድ የመቅሰፍት ኃይል በማየት ወደ  ማጥላላት ዞሩ እንጂ፡፡
የግድቡ መሠራት ለሱዳንም ሆነ ለግብጽ ቋሚና የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንደሚያስገኝ፣ አደጋ ሳይሆን ጥቅም መኖሩን ኢትዮጵያ አጠንክራ ለማስረዳት ብትጥርም፣ በተለይ ግብፆች የሚሰማ ጆሮ፣ የሚያገናዝብ አእምሮ ያገኙ አይመስልም፡፡
መረዳት የተቸገረው አእምሮአቸው ግን ጥያቄ በመጫር ሰነፍ ስላልነበረ የግድቡ ዝርዝር ጥናት ተሰጥቶን በራሳችን ባለሙያዎች እናስፈትሸው የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡ ይህን ጤነኛ ያልሆነ ጥያቄ፣ ትክክለኛ አላማና ፍላጐት የተረዳው የኢትዮጵያ መንግስት “ ሲያምራችሁ ይቅር” የሚል ቁርጥ ያለ መልስ በመስጠት ምራቃችው አፋቸው ውስጥ እንዲደርቅ አደረጋቸው፡፡
ምን እየሠራች እንደሆነ የምታውቀው ኢትዮጵያ፣ ያለባቸውን ስጋት ማጥፋት ካልሆነም መቀነስ ይችሉ ዘንድ አንድ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ ስለታላቁ የሕዳሴ ግድብ እንዲያጠና ፈቃደኛነቷን  አሳየች። እያንዳንዱ አገር ከየራሱ ሁለት ሁለት ሰው እንዲያቀርብ፣ በሶስቱም አገራት ተቀባይነት ያገኙ ሌሎት አራት ሰዎች በቡድን ውስጥ እንዲካተቱ ተደረገ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ አቋሟ በድምጽ የሚተላለፍ ውሣኔ ቢኖር የበላይነቱን እንደምትይዝ ልብ ይሏል፡፡ ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ በውሣኔዋ ገፍታ አለም አቀፍ የሙያተኞች  ቡድን ወደ ሥራ እንዲገባ ተደረገ፡፡ ቡድኑ ሥራውን እስኪያጠናቅቅ ለመጠበቅ ትዕግስት ያጡት ግብፆች፤ ኢትዮጵያን መረጃ እየደበቀች ነው በማለት ከሰሱ፡፡ ከአንድ ጊዜም ሶስት ጊዜ ግድቡ በሚሠራበት ቦታ በመገኘትና ሂደቱን ለመከታተል የቻለው አለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን፤ ሥራውን አጠናቆ ለሶስቱም መንግስታት ሪፖርቱን አስረከበ፡፡ ሱዳንና ኢትዮጵያ ለሪፖርቱ ቀና አስተያየት ሲሰጡ፣ ግብጽ ብቃት ይጐለዋል በማለት አጣጣለችው፡፡
አለም አቀፉ የሙያተኞች  ቡድን፤ ሪፖርቱን ለየሀገራቱ መስጠት እየተዘጋጀ ባለበት ጊዜ፣ የግድቡ ሥራ ከአንድ ደረጃ ላይ እየደረሰ ስለነበር፣ አባይ ድሮ ይፈስበት ከነበረው ወጥቶ አዲስ በተሠራለት መስመር እንዲፈስ ተደረገ፡፡ ግብፆች በዚህም ተናደዱ። በግብጽ የወቅቱ ኘሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ የሚመሩት የእስላም ወንድማማች ፓርቲ ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር ስብሰባ ተቀምጦ ስብሰባውም በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት እንዲተላለፍ ተደረገ። በዚህ ስብሰባ ላይም  በአሁኑ ወቅት ከስልጣን ተወግደው በእሥር ላይ የሚገኙት መሐመድ ሙርሲ ነገሩን በድርድር ለመጨረስ እንደሚፈልጉ ጠቁመው “አስፈላጊ ከሆነ ግን እያንዳንዷን የአባይ ጠብታ ውሃ በደም ጭምር እናስከብራለን” ሲሉ ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በዲኘሎማሲያዊ ቋንቋ ተገቢ እርምጃ ከመውሰዱ በላይ፣ ባልሳሳት ተወካዮች ምክር ቤት ደርሶ እየተንከባለለ የነበረው የናይል ተፋስስ አባል አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሕግ ሆኖ እንዲጸድቅ አደረገ፡፡ ስምምነቱ የመጨረሻ ጉዞውንም ጀመረ፡፡ አሁን ኡጋንዳም አጽድቃለች፡፡ ሌሎች እየተጠበቁ ናቸው፡፡
የባለሙያዎች ቡድን ያደረገውን ጥናት ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሶስቱ አገሮች የጋራ ስብሰባ ከብዙ  መጓተት በኋላ ካርቱም ላይ ሲጀመር፣ ግብፆች አሁንም የተለመደውን ፈቃደኝነት የማጣት  ባህሪያቸውን ይዘው ቀረቡ፡፡ የትናንት አጋራቸው ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ አቋም በማዘንበሏ፣ እንደ ከዳተኛ ቆጥረው ከመዝለፋቸውም በላይ፣ (የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ንግግር አስበው ሊሆን ይችላል)፣  በግድቡ ሥራ በቀጥታ ለመሣተፍ እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ይህንንም ተከትሎ ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን እንዲቀንስ፣ የሚያመነጨው የኃይል መጠንም በዚያው መጠን እንዲያቀዘቅዝ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ይኸኛውም ፍላጐታቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት፤ ግብፆች ቢሰሙትም ባይሰሙትም  የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ለአንድ ሴኮንድ እንኳ እንደማይቆም በተደጋጋሚ ተናገረ፡፡
ግብፆች ግን አልተዋጠላዋውም፡፡ የግድቡ ግንባታ በ30% ተጠናቋል የሚለውን የመንግስት መግለጫ “ውሸት” ነው ማለት ያዙ፡፡ ሕዝቡ ድሀ ስለሆነ መንግስትም የገንዘብ አቅም ስለሌለው ግንባታው መቆሙ አይቀርም ሲሉም ተነበዩ፡፡ መንግስት ቀድሞ ነገሩን “የጠላት ወሬ ነው” አለው እንጂ እኔ የሚኖረኝ መልስ “ልክ ናችሁ እንዲያውም ከመሬት አልተነቃነቀም” የሚል በሆነ ነበር፡፡ በአገራችን “ሽል ከሆነ ይገፋል ቂጣ ከሆነ ይጠፋል” የሚል ምሣሌ አለና ጊዜ ለሚመሰክርው ጉዳይ የማንም ራስ ሊታመም አይገባውም ማለቴ ነው፡፡ ለዚህኛውም የግብፆች ቧልት የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው መልስ፣ “በድጋሚ ቁርጣችሁን እወቁ” የሚል ዓይነት ነበር፡፡ “በሚቀጥለው ዓመት ግድቡ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል” የሚል መግለጫ መስጠት   ትርጉሙ ይሄው ነው። እስከአሁን ላነሷቸው ጥያቄዎችና ፍላጐቶች በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ያጡት ግብፆች፤ “ማንም ከማድረግ አያድንም” ወዳሉት እርምጃ ገብተዋል፡፡  
አዲስ ባረቀቁትና 98% የሕዝብ ይሁንታ አግኝቷል በተባለው ሕገ መንግስታቸው ውስጥ ለአባይ (ናይል)  አንድ አንቀጽ በመስጠት፤ “መንግስት የአባይን (ናይልን) ወንዝ ደህንነት ይጠብቃል፤ ግብጽ በወንዙ ላይ ያላትን ታሪካዊ መብት ከማስከበሩም በላይ እስከመጨረሻው ድረስ ተጠቃሚ ያደርጋታል….” የሚል ሃሣብ እንዲካተት አድርገዋል፡፡ ይህ ቃል እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የግብጽ ባለሥልጣናት መግለጫዎች ተራና ዋጋ ቢስ ቃል አይደለም፡፡ በዚህ ህገ-መንግስት መሠረት የሚቋቋመው የግብፅ መንግስትና የመከላከያ ኃይሉ በአጠቃላይ የግብጽ ሕዝብና መንግስቱ የሚለፉለት ጉዳይ ነው፡፡ ግብጽና ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የሆነ የድንበር መዋሰን ባይኖራቸውም፣ እንዲህ በቀላሉ ወታደራዊ ወረራ ያካሂዳሉ ተብሎ ባይታሰብም፣ ብዙ ደባ ለመጠንሰስ ግን የሚያገለግል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት እንዲሁም የአለም አቀፍ ግንኙነቷን በማደናቀፍ፣ ይህን ሁሉ የምናደርገው በሕገ መንግስታችን ተደነገገውንና ግብጽ በአባይ ላይ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው ሊሉን ይችላሉ። አሁንም የጀመሩት ስለሆነ ወደ ኋላ ይመለሳሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ይህ የግብፆች “አዲስ የምስራች”፤ ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ አዲስ ነገር ይዞ አልመጣም፡፡ የቀድሞውንና ያለውን እውነት ነው ያጐላው፡፡ አዲሱ ህገ መንግስት፤ ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ተደራድራ፣ የግብጽን አቋም ለመለወጥ  የምታደርገው ጥረት ብዙም ለውጥ እንደማያመጣ ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ሌሎች የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ፈራሚ አገሮች፣ ይህን የግብጽ ሕገ መንግስት እንደ ተራ ጉዳይ ሊያዩት የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ጉዳዩን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መድረኮች ላይ በማቅረብ መወያያና መከራከሪያ ሊያደርጉት፣ ያረገዘውን ደባም ሊያጋልጡ ይገባል፡፡ ይሄ ህገ መንግስት ነገ የሚያመጣውን መዘዝ አለም እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡


Published in ህብረተሰብ

የቻይና አምባሳደር ሞባይላቸውን ስለመሰረቃቸው ምን ይላሉ ?  
በጥምቀት በዓል በስርቆት ላይ ከተሰማሩት መካከል 26ቱ ተይዘዋል
 የጽዳት ችግር እንዳለ አምነዋል፣ “ከተማዋን  ጽዱ ለማድረግ እየሰራን ነው”
በየአዝማሪው ቤት በህፃናት ማስታወቂያ የሚያሰሩ ቢራ ፋብሪካዎችን ወቅሰዋል   

አቶ ጌትነት አማረ ይባላሉ፡፡ የጐንደር ከተማ ከንቲባ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት በምርጫ ተወዳድረው ከንቲባ ከመሆናቸው በፊት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ  በምክትል ከንቲባነትና በተቀዳሚ ምክትል ከንቲባነት አገልግለዋል፡፡ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽንና በዴቨሎፕመንት ማኔጅመንት ሁለት ዲግሪዎች ያገኙት ከንቲባው በኧርባን ማኔጅመንት ደግሞ የማስተርስ ድግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ለጥምቀት በዓል ወደ ጎንደር የሄደችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ የከተማዋን ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረን በቢሮቸው አግኝታ በተለያዩ የከተማዋ ጉዳዮች ላይ አነጋግራቸዋለች፡፡  

ጐንደር  ባሏት ታሪካዊ  ቅርሶች የተነሳ በአለም አቀፍና በአገር ውስጥ ቱሪስቶች በየጊዜው የምትጎበኝ ከተማ ናት፡፡  ከተማዋና ህዝቧ ከቱሪዝም ምን ያህል ተጠቃሚ ሆነዋል ይላሉ?
እንዳልሽው በየጊዜው በቅርሶቿ ከመጐብኘቷም ባሻገር በወርሀ ጥር፣ ጥምቀት በድምቀት የሚከበርባት ከተማ ናት፡፡ በመሆኑም ህዝቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግና የከተማዋን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ የአገር ውስጥና የውጭው አለም ጐበኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም በማሰብ፣ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የባህል ፌስቲቫል እያዘጋጀን ቆይተናል፡፡ በነዚህ ፌስቲቫሎች አገራችንን በደንብ ማስተዋወቅና የቱሪስቶችን ቁጥርም መጨመር ተችሏል፡፡ የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸውም አንፃራዊ በሆነ መልኩ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ሰሞኑን አይተሽ ከሆነ----አዳዲስ ሆቴሎች፣ ሎጆች፣ የባህል ምሽት ቤቶች እየተገነቡና እየተከፈቱ ቢሆንም አሁንም በቂ አይደለም፣ አሁን ባለው ሁኔታ አልጋ በቀላሉ ማግኘት አይቻልም፡፡ የቱሪስት ቁጥር መጨመር፣ የቆይታ ጊዜው መራዘምና መሰል ነገሮች ለከተማዋም ሆነ ለነዋሪዎቿ ተጠቃሚነት መጨመር ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ ለምሳሌ የታክሲና የባጃጅ ሹፌሮች ሰፊ ስራ ያገኛሉ፣ ባለሆቴሎች በምግብና በመኝታ በኩል ተጠቃሚ ናቸው፤ የባህል ቡና የሚያፈሉት፣ አዝማሪ ቤቶች፣ ሊስትሮ ሳይቀር-- የገቢ መጠኑ ይጨምራል። የስጦታ እቃ ሻጮች፣ ባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁስ አምራቾችም እንዲሁ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ባለሀብቱ ሎጅና ትልልቅ ሆቴል ለመገንባት ፍላጐት እያሳየ በመሆኑ ለነዋሪው የስራ እድል በመፍጠርም ሚናው የጐላ ነው፡፡
ሰሞኑን በከተማዋ ሶስት በዓላት (ዝግጅቶች) ነበሩ፡፡ አንዱ አመታዊው “አገር አቀፍ” የባህል ፌስቲቫል ሲሆን ሁለተኛው “ኢትዮጵያን በጐንደር” የተሰኘ አመታዊ ካርኒቫል ነው ሶስተኛው ጥምቀት፡፡ በዓላት እንዲህ ሲደራረቡ ለጐብኚዎች የሚደረገውን መስተንግዶ ጥራት አይቀንሰውም ?
አንደኛው በዓል በቅንጅት የተከበረ ነው፡፡ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ የባህል ማዕከልና በጐንደር ከተማ አስተዳደርና ባህል ቱሪዝም መምሪያ ማለት ነው፡፡ እኛ ይህንን በዓል ስናከብር አንደኛ የባህል ፌስቲቫሉ ሲከበር ነበር። እኛ ከዚያ ቀደም ብለን “ኢትዮጵያን በጐንደርን” ስናከብር ቆይተናል፡፡ ዘንድሮ ለየት የሚያደርገው አንድ አይነት አላማ የያዘ በመሆኑና ከቀድሞው ትንሽ የእንግዳ ቁጥር መጨመሩ ነው፡፡ ሌላው ልዩነት ዘንድሮ ከዘጠኙ ክልል እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ሰዎች መጥተው የእንግዳውን ቁጥር በተወሰነ መጠን ጨምረውት ነበር፣ እግዚቢሽንም ነበር፣ ከዚያ በፊትም ባዛር ነበረ፡፡ ባዛሩ “አዘዞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት” ለመገንባት የተዘጋጀ ነበር፡፡ እንዳልሽው በዓሉ ተደራራቢ ነው፤ አዎ ይሄ እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን የባህል ማዕከሉና የእኛ ከተማ አስተዳደር ያዘጋጀው በዓል በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው፡፡ ቀጥሎ ጥምቀቱ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ፍላጐት ምንድነው--- የቱሪስቱ ቁጥርም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ ቁጥር እንደሚጨምር ነው፡፡ በሌላው ዓለም ለምሳሌ ብራዚልን ብትወስጂ--- በሚዲያ እንደምንሰማው በዓመት አንዴ ለሳምንታት የሚያከብሩት ፌስቲቫል በዓመት ውስጥ የማይሰበስቡትን ገቢ ያገኙበታል፡፡ አላማውም ይሄው ነው፡፡
ሌላው አለም ምናልባትም በቂና የተደራጀ  የመስተንግዶ አገልግሎት የተሟላ ስለሚሆን በርካታ እንግዳ ቢጠራም  ተደራራቢ በዓላት ቢያዘጋጅም ችግር ላይገጥመው ይችላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ አገራት ግን የምንገነባውን ገጽታ እንዳናፈርሰው የሚያሰጋ ይመስለኛል ----
የሆስፒታሊቲውን ሁኔታ በተመለከተ አንዱና ዋነኛው ነገር፣ በባህልና ቱሪዝም በኩል አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በስልጠና ማገዝ፣ ሁለተኛ ሰርቪሱን መጨመር ከተቻለ ለጐንደር ከዚህም በላይ እንግዳ መጥራት ይቻላል፡፡ ጀማሪ ከመሆናቸው አኳያ በግንዛቤ እጥረትና በልምድ ማነስ የተነሳ መስተንግዷቸው አርኪ ላይሆን ይችላል እንጂ እንግዳው ስለበዛ፣ በዓል ስለተደራረበ ሆስፒታሊቲ መጥፎ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ግንዛቤና ልምድ ከሌለ ጥቂት እንግዳ መጥቶ መስተንግዶውና ሁኔታው ላይመቸውና ቆይታውንም ላያራዝም ይችላል፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ በልምድና በስልጠና በሆስፒታሊቲ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትን ማስተካከል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በ2003 ዓ.ም በተደረገው አጠቃላይ የመስተንግዶ ግምገማ፣ 2004 ዓ.ም እና 2005 ዓ.ም ላይ የተሻሉ የመስተንግዶ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከባለፈው ዓመት የዘንድሮው የተሻለ እንደሆነ አምናለሁ፣ ስለዚህ በዓላት መደራረባቸው ሳይሆን የግንዛቤው ጉዳይ ነው  ሆስፒታሊቲው ላይ ችግር የሚፈጥረው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዓላት ተደራርበውም ግን  ያን ያህል ጐንደር በእንግዳ ተጥለቀለቀች ለማለት ያስቸግረኛል፡፡ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት፣በበዓላቱ መደራረብ ከወትሮው የእንግዳ ቁጥር ትንሽ ጨምሯል፡፡ በሌላው ዓለም እኮ በአንድና በሁለት ቀን የሚገባው ቱሪስት መጠን የሚያስደነግጥ ነው፡፡
እርስዎ የሚያውቁት ቱሪስት የሚጎርፍበት የአለም ከተማ አለ?
እኔ በቅርቡ እስራኤል አገር ሄጄ ነበር፡፡ እየሩሳሌም ኦልድ ሲቲ የሚባል ቦታ አለ፡፡ በአንድ ቀን የሚገባው ቱሪስት አካባቢውን የሚያጨናንቅ ነው፡፡ ታሪካዊ ቦታዎችን ለማየት ወረፋው በጣም በጣም የሚያታክት ነው፡፡  ያንን ያየ ሰው፣ጐንደር እንግዳ ያጨናነቃት፣ አስተናጋጆች መውጫ መግቢያ አጥተው የሚዋከቡባት ናት ሊል አይችልም፡፡ ነገር ግን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተፈለገው ደረጃ ተገንብተው፣ በጥራት ደረጃቸውም ልቀው ሄደዋል ለማለት አንችልም፡፡ ይሄ ቀስ በቀስ ከልምድም ከኢኮኖሚ አቅምም ጋር ተያይዞ የሚስተካከል ነው፡፡
ህዝቡ ከቱሪዝሙ ተጠቃሚ ሆኗል ብለውኛል፡፡ ቱሪስቱ የሚመጣው ቅርሶች ስላሉ ነው፡፡ ነገር ግን ህዝቡ ለቅርሶቹ ያን ያህል ጥንቃቄና ጥበቃ ያደርጋል የሚል እምነት አላደረብኝም፡፡ አንዳንድ ታሪካዊ ቅርሶች በጥንቃቄ ጉድለት ጉዳት ደርሶባቸው ይስተዋላል፡፡ የአስተዳደሩ  ጽ/ቤት  ህዝቡ በቅርስ አጠባበቅ ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ምን ያህል ጥረት አድርጓል?
ትክክል! አንደኛ በባለቤትነት የጐንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም አለበት፡፡ ከእኛ ጽ/ቤት ጋር በትብብር የሚሰሩም አሉ፡፡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ቅርሱ እንዲጠገንም እንሰራለን፡፡ ሁለተኛ ቅርሱን ለመንከባከብ፣ ጥፋት እንዳይደርስበት የምንሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በፊት የሰርግ ስነስርዓት ሲኖር፣ በፋሲል አብያተ መንግስታት ጭፈራና የሞንታርቦ ጩኸት ይደረግበት ነበር፡፡ ድምፁና ጭፈራው ቅርሱን እንዳይጐዳው ያንን ማስቀረት ችለናል፡፡ እዛው አካባቢ ባዛርም ይካሄድ ነበር፡፡ መስቀል አደባባይ ላይ ሁከቱና  ባዛሩ ቅርሱን እንዳይጐዳው እሱንም አስቀርተናል፡፡ የፓርኪንግ ስራም ነበረው፡፡ አሁን በአካባቢው ምንም ስራ አይሰራም፡፡ በከተማ አስተዳደሩ በኩል የጐደሉ ነገሮችን ማስተካከሉ እንዳለ ሆኖ ቅርሶችን የመንከባከብ ስራ እየሰራን ነው፡፡ ከግንዛቤም አኳያ አጠቃላይ ለህዝቡ ግንዛቤ ፈጥረናል ብለን አናስብም፣ ግን በዘርፉ እየተሰሩ ያሉና የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ የአመቱን እቅዳችንን ለፈፃሚ አካላት በምናስተዋውቅበት ጊዜና በተለያዩ ዎርክሾፖች ላይም ቅርሱን መታደግ የከተማ አስተዳደሩና የተወሰኑ አካላት ብቻ ሳይሆን የህዝቡም እንደሆነ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የጀመርናቸው እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን የተሟላ ግንዛቤ ህዝቡ ልብ ውስጥ አኑረናል የሚል እምነት የለንም፡፡ በቀጣይ ከፍተኛ ስራን መስራት ይጠይቃል ማለቴ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /UNESCO/ አንድ ቅርስ የአለም ቅርስ ነው ብሎ ሲመዘግብ የቅርሱን ዙሪያና አጠቃላይ ድባብ /Buffer Zone/ ብሎ ይከልላል። በፋሲል አብያተ መንግስታት ዙሪያውን ያሉ የድሮ ክብክብ ድንጋይ ቤቶች በባፈር ዞኑ የተከለሉ ይመስለኛል፡፡ እዛ አካባቢ ግን ስጋቶች አሉ?
ምን አይነት ስጋቶች ናቸው?
ሰሞኑን በእንኮዬ በር በኩል እነ እመት አበቅየለሽ መንደር ሄጄ ነበር፡፡ እዛ አካባቢ ያሉ የድንጋይ ክብክብ ጥንታዊ ቤቶች ሲፈርሱ ነበር፡፡ የህንጻ ግንባታ ሊካሄድ ነው የሚል ስጋትም አለ፡፡ ይሄ ከዩኔስኮ ጋር አያጋጫችሁም?
ጥሩ! አንደኛ በጐንደር ከተማ ላይ እየሰራን ያለነው ስራ ምንድነው---ህንጻ በአካባቢው ሲገነባ ከፍታው አልፎ አልፎ ችግር ነበረው፡፡ ይህ የሆነው ከግንዛቤ ማነስ ነው፡፡ የፋሲልን አጠቃላይ እይታ የሚከልሉ ፎቆች ተሰርተው ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት አመታት የባህል ፌስቲቫሎቹን ስናከብር እግረ መንገዱን ልዩ ልዩ የፓናል ውይይቶች ይካሄድ ነበር፡፡ እዚያ ላይ ትኩረት ሰጥተን ያየነው ነገር ምንድነው--- በግንቡ ዙሪያ እይታውን የሚከልሉ ፎቆች በተሰሩ ቁጥር፣ ግንቡ ቱሪስትን የመሳብ አቅሙ ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪም ዩኔስኮ ከዝርዝር ውስጥ ያወጣዋል የሚለውን ጉዳይ ተመልክተናል፡፡ ከዚያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጡ ምሁራን ጋር በመተባበር በተደረገ ውይይት፣ ከግንቡ በተወሰነ ሬዲየስ ላይ የሚገነቡ ፎቆች ከፍታ መጠን እንዲወሰን የሚያደርግ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ሌላው ቅድም ያልኳቸው እንኮዬ መስክ አካባቢ ያሉ ቤቶች እንዳይፈርሱ ጥብቅ ክትትል እናደርጋለን። ሌላው ቀርቶ ፊት ለፊት ቅድም ያየሻቸው ቤቶች በመኖራቸው፣ የጐንደር ዋና ዋና መንገድ አይተሽው ከሆነ ድሮ በጣሊያን የተቀየሰ ነው፡፡ በዚያ ምክንያት ትንሽ የትራፊክ መጨናነቅ አለ፡፡ አሁን የእግረኛ መንገድ እየሰራን ነው፡፡ መንገዱን ስንሰራ እነዚህን የድንጋይ ክብክብ ቤቶችን አገኘን፡፡ እነዚህን ቤቶች ማፍረስ በቅርሱ ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ስለምናውቅ እንዳይነካ አድርገናል፡፡ እንኮዬ መስክ ላይ ያሉ ተመሳሳይ ቤቶችንም እንዲሁ የምንነካበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ሁለተኛ የኮር ዞንና በፈር ዞን የሚለውን በተመለከተ  ከፌዴራልም ከክልሉም ጋር እየተነጋገርንበት ነው፡፡ ባለሙያዎችም ያጠኑት ነገር አለ፡፡ በፈር ዞኑ እስከየት ድረስ ነው? የሚለውን ጉዳይ ማለት ነው፡፡ የት የት ድረስ መከለል አለበት የሚለውንም ያጠኑት ባለሙያዎች ለከተማው ባህልና ቱሪዝም ገልፀዋል፡፡ በቅርቡም ለከንቲባ ኮሚቴ ቀርቦ መልክ የምናስይዘው ይሆናል፡፡
ቀደም ሲል የመፍረስ ስጋት ብቻ ሳይሆን ይፍረሱ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶ ላለፉት ስድስት አመታት ክርክር ላይ ያሉ ባለ ይዞታዎችን አግኝተናል፡፡ “እነዚህ ደብር ያላቸውና ከግንቡ ጋር ልዩ ታሪክ ያላቸው በመሆኑ ሊፈርሱ አይገባም፣ ሲፈርሱም ከ300 ሰዎች በላይ ይፈናቀላሉ” ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ይህን ያውቃሉ?
የምትይውን ቦታ በትክክል አላወቅኩትም ነገር ግን ዩኔስኮ እንዲጠበቁ በበፈር ዞን የያዛቸው ቤቶች እንደማይሆኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሌላው ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ እዛ አካባቢ ፎቅ ይገንባ ቢባል እንኳን የከፍታው ሁኔታ የተመጠነና የግንቡን ሁኔታ በማይከልል ሁኔታ ነው፡፡ ይፈርሳል የሚባሉ ቤቶች  ካሉም ዝም ብሎ በግለሰቦች የተያዙ ነገር ግን ከተማዋ ደረጃዋን የጠበቀች እንድትሆን የመልስ ማልማት ስራ የሚካሄድባቸው ይሆናሉ እንጂ እነዚህ ዩኒስኮ ጥብቅ ያደረጋቸው “ጅጌ” የተባሉት ክብ የድንጋይ ቤቶች አይነኩም፡፡ የቀበሌ ቤቶች ይኖራሉ- በግለሰብም የተያዙ ሆነው ጐስቋላ ቤቶች፡፡ እነሱ ለመልሶ ማልማት ሊፈርሱ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ አበባም ሆነ ሌላ የትኛውም ከተማ ላይ የሚካሄድ ነው፡፡
ሌላው የአካባቢው ነዋሪዎች ያነሱት ቅሬታ “እዛው መንደር ውስጥ እመት አበቅየለሽ ጠጅ ቤት ፊት ለፊት አቢሲኒያ ባንክ ያለበት ህንፃ የተገነባው ሌሎች ጥንታዊ ቤቶች ፈርሰው ነው፡፡ የህንፃው ሶስት አራተኛ ክፍል ግን አልተከራየም፡፡ ሰው ከቦታው የተፈናቀለው በከንቱ ነው” የሚል ነው፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
ያልሽው ህንፃ ከተገነባ ቆይቷል፡፡ ያን ጊዜ እኔም አልነበርኩም፡፡ ግን ህንፃው ሲገነባ የምትያቸው ጥንታዊና መፍረስ የሌለባቸው ቤቶች እንደፈረሱ የሚያሳይ ሪፖርት የለም፡፡ በየሶስት ወሩ ህዝቡን በሲኒማ አዳራሽ እያገኘን እንወያያለን፡፡ ሆኖም እንዲህ ዓይነት ቤቶች ፈረሱ የሚል ቅሬታ ሳይሆን ቅድም ከቅርስ ጥበቃ ጋር ያነሳሽው አይነት ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ይህ ማለት እንዴት ቅርሶች ከጉዳት ይጠበቁ፣ ህዝቡ እንዴት የባለቤትነት ስሜት ይሰማው በሚልና በመሰል ጉዳዮች ህዝቡ ሃሳቦችን እያነሳ እንወያያለን፡፡ አሁንም አቢሲኒያ ባንክ ያለበትን ህንፃ በተመለከተ በፋሲል ግንብ ፊት ለፊት እንደመሆኑ ከG+1 በላይ እንዳይገነባ በወቅቱ የነበረው አመራር መከልከል ነበረበት፡፡
ግን እኮ ህንፃው ባለሶስት ፎቅ ነው?
ትክክል ነው፣ ሶስት ፎቅ ነው፡፡ ይህንን እንደ ስህተት ነው የምንወስደው፣ አሁንም የማረጋግጥልሽ ለቅርስ ተብለው የተያዙ ቤቶች አይፈርሱም። ከዚያ ውጭ ያሉ የግል ጐስቋላ የቀበሌ ቤቶች በመልሶ ማልማት ግን ይፈርሳሉ፡፡
ከተማዋ የአለም አቀፍ ቱሪስቶች መዳረሻ ከመሆኗ አንፃር  ጽዳት ይጐድላታል፣ የሚሸቱ ቱቦዎች አሉ፣ ይሄ ደግሞ ቱሪስቶችን ያሸሻል፡፡ ይሄን ለማሻሻል ምን አስባችኋል?
ትክክል ነው፣ የጽዳት ችግር አለ፣ ግን ጽዱ ለማድረግ እየሰራን ነው፡፡
ለምሳሌ ምን አይነት ስራዎች?
ለምሳሌ አንዱ ያደረግነው ነገር ምንድነው--- የደረቅ ቆሻሻ ማኔጅመንቱ በፊት በማዘጋጃ ቤቱ ነበር የሚካሄደው፡፡ ነገር ግን ውጤታማ ባለመሆኑ፣ እንዲህ አይነት ስራዎችን በሌላ አካል (አውት ሶርስ) በማሰራት የስራ እድል መፍጠርና ህዝቡንም ማሳተፍ ይቻላል በሚል ከባለፈው አመት ጀምሮ በምክር ቤታችን አጽድቀን እየተሰራበት ነው፡፡ እዚህ ላይ ያጋጠመን ችግር ማህበራቱ የጠነከሩ አለመሆናቸው  ነው፡፡ አንደኛ ተሽከርካሪ የላቸውም፣ ተከራይተው ነው የሚሰሩት፡፡ ሁለተኛ የልምድም ማነስ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ እንቅፋት ሆኗል፡፡ አሁን የትኛውን አማራጭ እንጠቀም የሚለውን እያጠናን ነው፡፡
ሁለተኛ ከፍሳሽ ቱቦዎች መሽተት ጋር ያነሳሽው ችግር፣ ብዙዎቹ በተለምዶ ፒያሳ በሚባለው አካባቢ ያሉት ድሮ በጣልያን ጊዜ የተሰሩ ፍሳሽ ማስወገጃዎች በመሆናቸው የመጣ ችግር ነው። ከባለፈው አመት ጀምሮ የእግረኛ መንገድም የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይዎችም እየሰራን ነው፡፡ እሱን ስንሰራ ሴፕቲክ ታንካቸው በቀጥታ ከድሬኔጅ ጋር የተገናኘ ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ እነዚህ ችግሮች በአብዛኛው ያለባቸው ቤቶችና አካባቢዎች የኪራይ ቤቶች ይዞታ ናቸው፡፡ አሁን ሳያልቅ ስለመጣችሁ ነው እንጂ እሱን የማስተካከል ስራ ጀምረናል፡፡ ሴፕቲክታንክ እንዲቆፈር፣ ከድሬኔጅ ጋር የተያያዙ ስዌሬጆች እንዲላቀቁ የማድረግ ስራ ተጀምሯል፡፡ አንቺ እንዳልሽው የተወሰኑ ቅሬታዎች ይደርሱናል፣ ነገር ግን ኪራይ ቤቶች በቅርቡ እልባት ይሰጠዋል ብለን እናምናለን፡፡ በአጠቃላይ ያለውን የከተማ ጽዳት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ፣ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የፍሳሽ ማስወገጃ መኪኖችን ገዝቶ በቅናሽ ዋጋ ለማህበረሰቡ መስጠት ጀምሯል። ያየሽውና የጠየቅሽው ትክክል ነው፡፡ ጐንደር ከተማ በተፈለገው ደረጃ አልፀዳችም፡፡ ግን ይህንን ለማስተካከል እየተሰራ ነው፡፡  
ሌላው እጅግ አሳሳቢው ነገር የቢራ ፋብሪካዎች የፉክክር ትንቅንቅ ነው፡፡ በየምሽት ቤቱ ቢራዎችን እየጠጡ የሚያስተዋውቁት 18 አመት ያልሞላቸው ታዳጊዎች ናቸው፡፡ በሁሉም ቢራ በሚሸጥባቸው  ምሽት ቤቶች ቢራ ስፖንሰር ያደርጉና “ይሄ የእከሌ ቢራ ቤት ነው ይሄኛው ራስ ምታትና ሀንግኦቨር አለው” እያሉ ህፃናቱ ሲናገሩ አንገት ያስደፋል። ይህን ጉዳይ የእርስዎ ጽ/ቤት ያውቀዋል? ይሄ ትውልዱን ወዴት ይወስደዋል?
ይሄ ጉዳይ ከማስታወቂያ አለጣጠፉ ጀምሮ ቅድም ያልሽውን ነገር ያመጣል፡፡ አሳሳቢም ነው። ሰሞኑን ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በየኮርነሩ ያለው ማስታወቂያ ይገርማል፡፡ የነፃ ገበያ አስተሳሰብና ግንዛቤ ልክ እንዳልሆነ እየገባን ነው፡፡ በቀደም ዕለትም በጨረፍታም ቢሆን አሁን አንቺ ያልሽኝን ነገር ሰምቼዋለሁ፡፡ አንድ የቢራ ኩባንያም ሆነ ሌላ ባለምርት ምርቱን ማስተዋወቅ ያለበት ተጽእኖ በማሳደር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ዳሽን ምርቱን ለማስተዋወቅ የራሱ ጋርደኖች አሉት፡፡ አሁን በየምሽት ቤቱ ህፃናቱን እያሰማሩ እንዲህ አይነት ስራ ስለማሰራታቸው በጨረፍታ ሰምቻለሁ፡፡ ስህተቱ ግን የወጣቶቹ ነው የሚል እምነት የለኝም። ይህ ችግር የቢራ ኩባንያዎቹ ነው፡፡ የቅስቀሳውም ሁኔታ ትክክል አይደለም፡፡
በአንድ የአዝማሪ ምሽት ቤት “ይሄን ቢራ አትጠጡ ራስ ምታት አለው” እያሉ ህፃናት ልጆች ሲናገሩና የሚያስተዋውቁትን ቢራ እየጠጡ ሲጨፍሩ እዚያው ሆኜ በዓይኔ አይቼአለሁ---
ለዚህ ችግር በአስቸኳይ  እልባት መስጠት ይኖርብናል፣ ካልሆነ ችግሩ የከፋ ይሆናል፡፡ የትኛውም ቢራ ሲያስተዋውቅ አግባብ በሆነ መንገድ እንጂ ሌላውን እያጥላላና ተጽእኖ እየፈጠረ መሆን የለበትም፡፡ አንዱን እየጠጡ፣ ሌላውን  ይፈልጥሃል  ይቆርጥሃል፣ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ይሄ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ ዳሽን ብቻ የሚሸጥበት ወይም ሜታ ብቻ የሚሸጥበት ሆቴል የለም፡፡  ሁሉም ቢራ ይሸጣል፡፡ ሰው የሚፈልገውን መርጦ ይጠጣል ወይም የራሳቸው ቢር ጋርደን ሊኖራቸው ይገባል። በእርግጠኝነት የምነግርሽ ግን የእኛ ንግድ መምሪያ አለ፡፡  
በመምሪያው በኩል አቅጣጫ እናስቀምጣለን። በሌላ በኩል የኩባንያዎቹን ተወካዮች ጠርተን ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ እንሰጣለን፡፡  ጉዳዩ ችላ የሚባል አይደለም፡፡ ጥቆማውና መረጃው ግን በጣም ይጠቅመናል፡፡ ይሄ ጉዳይ አይቀጥልም፡፡ በቅርቡ  ህጋዊ እርምጃዎችን እንወስዳለን፡፡
የጥምቀት እለት የቻይናውን አምባሳደር ጨምሮ በርካታ እንግዶች ሞባይል፣ ካሜራ፣ ፓስፖርትና ሌሎች ንብረቶች ተሰርቆባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የፀጥታና ደህንነት ስራው ላይ ክፍተት እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡ በበዓሉ ላይ ምን ያህል ንብረት እንደተሰረቀ መረጃው አለዎት? በዕለቱ የሶስት የካሜራ ጋዜጠኞች ሞባይል መጥፋቱንም አውቃለሁ፡፡ ይሄ የጎንደርን ገፅታ አያበላሽም?
ይህን በዓል ስናስብ በተለይ የፀጥታ አካሉ እና የአስተዳደር ፀጥታ፣ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ዝግጅት አድርገዋል፡፡ በበዓሉ ብቻ ሳይሆን ቱሪስቶች በየጊዜው ስለሚገቡና ስለሚወጡ አመቱን ሙሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ እሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀደም ሲል የጠቀስሻቸው ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ይህም የተከሰተው ጥምቀተ ባህሩ ላይ የሚገባው ህዝብ ከመጠን በላይ የተጨናነቀ ስለነበረ ነው። እዛ ላይ የሞባይል እና የመሳሰሉ እቃዎች ንጥቂያ ተፈጽሟል፡፡ የሚገርምሽ ከሰዓት በኋላ ብዙዎቹ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡
ስንት ይሆናሉ እጅ ከፍንጅ የተያዙት?
27 ናቸው፡፡ የሚገርምሽ ይህን በዓል በማሰብ ከሌላ ክልል ተደራጅተው መጥተው ነው የያዝናቸው፡፡ 13 ያህል ተንቀሳቃሽ ስልክ እጅ ከፍንጅ ተይዞ ለባለቤቶቹ ተመልሷል፡፡ ፓስፖርትና መንጃ ፍቃድ ተመልሷል፡፡ ከ27ቱ ውስጥ  የዚህ ከተማ ነዋሪ ሆኖ ያገኘነው አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ ከ26ቱ ደግሞ 11ዱ ከአንድ ክልል የመጡ ናቸው፡፡
እኔ ጐንደር ከመጣሁ ዛሬ ዘጠነኛ ቀኔ ነው፡፡ እስካሁን መብራት ጠፍቶ አያውቅም፣ ውሃም ሄዶ አላየሁም፣ የኢንተርኔት አገልግሎቱም ግሩም ነበር፣ ነገር ግን አንዳንድ ነዋሪዎች በከተማዋ  የውሃ ችግር እንዳለና በየተራ ውሃ እንደሚያገኙ፣ መብራት እንደሚቆራረጥ የሚናገሩ አሉ፡፡ ለበዓሉ እና ለእንግዶች ሲባል በውሃና መብራት ላይ ጥንቃቄ ተደርጐ ነው? ወይስ--
Thank you! ጐንደር ላይ አንዱ ቅሬታ የውሃና የመብራት መቆራረጥ ችግር ነበር፡፡ የችግሩ መንስኤ የውሃም ሆነ የመብራት አለመጠገን ነበር። የሚገርመው ከባለፈው አመት ሚያዚያ በፊት በሳምንት በአማካይ ሶስትና አራት ጊዜ መብራት ይጠፋ ነበር፡፡ ይህንን ለማስቀረት ከሰሜን ምዕራብ ሪጂን መብራት ሃይል ጥገና ክፍል ጋር በመነጋገር ከፍተኛ ስራ ሰርተናል፡፡ በፊት መቆራረጥ ብቻ ሳይሆን  ሃይል የለውም፡፡ በተለይ ትልልቅ ሆቴሎች ላይ ደብዛዛ ሆኖ ነበር የሚበራው፡፡ በዚህ ምክንያት ለተከታታይ ሶስት ወራት ጥገና ተካሄደ፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ ጐንደር ላይ መብራት አይጠፋም፡፡ በውሃም በኩል ከአንገረብ ወንዝ ውሃው የሚገፋው በኤሌክትሪክ ፓምፕ ስለነበር መብራት ሲቋረጥ ውሃም ይቋረጥ ነበር፡፡ ከባለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ ግን የውሃም የመብራት መቋረጥም በእጅጉ ቀንሷል፡፡


Published in ህብረተሰብ
Page 2 of 14