የግብፅን የናይል ታሪካዊ መብቶች ያስጠብቃል በሀይማኖት፣ በዘር፣ በፆታ እና በአካባቢ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት አይቻልም የግብፅ የጦር ኃይል አዛዥ በምርጫው ይወዳደራሉ

ከግብፅ የታህሪር አደባባይ አብዮት በኋላ የተደረገውን ምርጫ አሸንፈው ስልጣን ላይ የወጡት “የሙስሊም ወንድማማቹ” ሞሀመድ ሙርሲ፤ በአጭር የስልጣን ዘመናቸው ህዝበ ውሳኔ ተግባራዊ አድርገውት የነበረው የ2012 ህገመንግስት ሰሞኑን በተደረገው የህገመንግስት ሪፈረንደም ተሽሯል። የሞርሲ ህገመንግስት አጭር ጊዜ ስራ ላይ የዋለ ቢሆንም ብዙ ውዝግቦችንና አለመግባባቶችን ማስነሳቱ አይዘነጋም፡፡ ሙርሲ ተግባራዊ ባደረጉት ህገመንግስት ውስጥ የተካተቱት አብዛኞቹ አንቀፆች እና አረፍተ ነገሮች በአዲሱ ህገመንግስት ተሰርዘዋል። ነገር ግን አዲሱ ህገመንግስትም የወታደሩን የበላይነት የሚያስጠብቅ ነው በሚል ትችቶች እየተሰነዘረበት ይገኛል፡፡ የናይል ጉዳይ በሁለቱም ህገመንግስቶች የተጠቀሰ ሲሆን አዲሱ ህገመንግስት ጠንከር ባለ አገላለፅ ነው ያስቀመጠው፡፡ በሙርሲ የፀደቀው ህገመንግስት “የናይል ወንዝ እና የውሀ ሀብቶች ብሄራዊ ሀብቶች ናቸው፡፡ መንግስት እነዚህን ሀብቶች ለመጠበቅ እና ለማልማት ቁርጠኛ ነው፡፡

እንዳይባክንም ይከላከላል፡፡ የውሀው አጠቃቀም በህግ ይወሰናል” ሲል ሰሞኑን የፀደቀው አዲሱ ህገመንግስት በአንቀፅ 44 ላይ ስለ ናይል የሚከተለውን ይላል፡- “መንግስት የናይል ወንዝን ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነው፡፡ የግብፅን ታሪካዊ መብቶች ያስጠብቃል፡፡ የናይል ተጠቃሚነትን ያሳድጋል። ውሃው እንዳይበከል እና እንዳይባክን ያደርጋል፡፡ የማእድን ውሃውን ለመጠበቅና የውሀውን ደህንነት ለማስጠበቅ በመስኩ የሚካሄደውን ሳይንሳዊ ምርምሮች ይደግፋል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ የናይልን ወንዝ የመጠቀም መብት አለው፡፡ ውሀውን ያለአግባብ መጠቀም ወይም አካባቢውን መጉዳት የተከለከለ ነው፡፡ ዝርዝሩ በሌላ ህግ ይደነገጋል፡፡” ሰሞኑን ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ አብላጫ ድምፅ እንዳገኘ የተነገረለት የግብፅ ህገመንግስት፤ ልክ እንደ ቀደምቶቹ የአገሪቱ ህገመንግስቶች መነሻው ያደረገው የ1971ን የአገሪቱን ህገመንግስት ነው።

አዲሱ ህገመንግስት ከአንድ አመት በፊት በመሀመድ ሞርሲ አጭር የስልጣን ዘመን በህዝበ ውሳኔ ከፀደቀው ህገመንግስት ጋር ቢመሳሰልም መሰረታዊ ለውጦች ተደርገውበታል፡፡ በመሀመድ ሞርሲ ዘመን ተግባራዊ በተደረገው ህገመንግስት፤ “አልአዝሀር” ለተባለው ተቋም የእስልምና ህጎችን በተመለከተ ህግ አውጭዎችን የማማከር ስልጣን ሰጥቶት የነበረ ሲሆን በአዲሱ ህገመንግስት ይህን ስልጣን ተነስቷል። የመከላከያ ሚኒስትርን በተመለከተ ሁለቱም ህገመንግስቶች የመከላከያ ሚኒስትር ወታደራዊ መኮንን እንዲሆን ሲደነግጉ፣ የአሁኑ ህገመንግስት እጩው በጦር ሀይሉ ከፍተኛ ምክር ቤት መፅደቅ እንዳለበት ይገልፃል፡፡ የምርጫ ኮታን አስመልክቶ የቀድሞ ህገመንግስት ገበሬዎች እና ሰራተኞች በታችኛው ምክር ቤት ቢያንስ የሀምሳ በመቶ መቀመጫ እንዲኖራቸው የሚደነግግ ሲሆን አዲሱ ህገመንግስት ከላይ ለተጠቀሱት ቡድኖች ተሰጥቶ የነበረውን መብት በዝርዝር ህግ ይገለፃል በሚል አልፎታል፡፡

በአዲሱ ህገመንግሥት በግብፅ ህገመንግስት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚመለከት አንቀፅ የተካተተ ሲሆን ከወሲብ ንግድ ጋር የተያያዘ እና ማናቸውም ህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከልከሉን ይደነግጋል፡፡ ማንኛውንም መልእክተኛ እና ነብይ መስደብ በወንጀል ያስቀጣል የሚለውን በሞርሲ ህገመንግስት ላይ የተካተተ አንቀፅ ሙሉ በሙሉ ያስወጣው አዲሱ ህገመንግሥት፤ የአለም አቀፍ ስምምነቶችን በተመለከተም በሰብአዊ መብቶች ዙርያ የተደረጉ እና የፀደቁ ስምምነቶች እንዲሁም ቃልኪዳኖች ተግባራዊ የሚሆኑት ታትመው ሲወጡ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ህግ አውጪውን አስመልክቶ የሞርሲ ዘመን ህገመንግስት ዋና አቃቤ ህግን የመሾምን ስልጣን ለፕሬዚደንቱ የሰጠ ሲሆን በአዲሱ ህገመንግስት ስልጣኑ ወደ የህግ ከፍተኛው ምክር ቤት ተዛውሯል፡፡ የሞርሲ ዘመን ህገመንግስት፤ ሴቶችን የወንዶች እህቶች በሚል ሲገልፅ፣ አዲሱ ህገመንግስት ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው የሚል ሲሆን፤ ሴቶችን ከማንኛውም አይነት ጥቃት ለመከላከል መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ይገልፃል፡፡ አዲሱ ህገመንግስት ሀይማኖትን፣ ዘርን፣ ፆታን እና አካባቢን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋም የተከለከሉ መሆናቸውን በመደንገግ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በላይኛው ምክር ቤት የነበረውን ቦታ ሙሉ በሙሉ ሽሮታል፡፡

ድብደባን በተመለከተ የበፊቱ ህገመንግስት ማንኛውም በእስር ላይ ያለ ግብፃዊ ድብደባ ሊፈፀምበት እንደማይችል ሲያስቀምጥ አዲሱ ህገ መንግስት ማንኛውም ግብፃዊ በማንኛውም ሁኔታ ድብደባ ሊፈፀምበት እንደማይቻል እና ድርጊቱም ወንጀል እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ሁለቱም ህገመንግስቶች የጦር ሰራዊት (የመከላከያ) በጀት በህግ አውጭው አካል እንዳይጠየቅ ከለላ ሰጥተዋል፡፡ አዲሱ የግብፅ ህገመንግስት የ2011 አብዮትን ሌጋሲ ያስጠበቀ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ከሀይማኖት የተለየ ህገመንግስት ነው ቢባልም በህገመንግስቱ የተካተቱ አንዳንድ አንቀፆች ግን የወታደራዊውን መንግስት አቋም የሚያጠናክሩና ግብፅን ወደ ወታደራዊ አገዛዝ የሚመልሱ ናቸው በሚል ትችቶች በስፋት እየተሰነዘሩ ነው፡፡ የቀድሞውም ሆነ አዲሱ ህገመንግስት ችግር “በሁለቱም ህገመንግስቶች የተንፀባረቀው የቡድን ስሜት እንጂ ግብፅን እንደ አገር ማእከል ያደረገ አይደለም፡፡

ህዝበ ውሳኔው ላይ የቀረበው ከእስልምና ወንድማማችነት እና ከመፈንቅለ መንግስት ወይም ከኢስላም እና ከሚሊተሪ የሚል ነው፡፡ በዚህ ሂደት ቅድሚያ የተሰጣት ግብፅ ሳትሆን ቡድኖች ናቸው” ይላሉ - ሁለቱንም ህገመንግስቶች የሚነቅፉት ወገኖች፡፡ የህገመንግስቱ ትልቁ ስህተት ይዘቱ ላይ ሳይሆን የተረቀቀበት አካሄድ ላይ ነው የሚሉት በእስራኤል የሚገኘው የመካከለኛው ምስራቅ ጥናትና ዲፕሎማሲ ምርምር ማዕከል ሊቀመንበር ዮራም ሜይታል ናቸው፡፡ እንደእሳቸው አገላለፅ፤ ህገመንግስቱ የተረቀቀበት መንገድ በወታደራዊው መንግስት እና በእስልምና ወንድማማችነት መካከል ያለውን የፖለቲካ ልዩነት መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ከማካተት ይልቅ ማስወጣት ላይ ያተኮረው አዲሱ ህገመንግስት፤ ስር እየሰደደ ያለውን የግብፃውያንን ልዩነት ለማከም የሚያስችለውን ቅመም አጥቷል ይላሉ፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን የአዲሱ ህገመንግስት መፅደቅ በቀጣይ በግብፅ ለሚደረገው ምርጫ መንገድ ይጠርጋል የተባለ ሲሆን የግብፅ የጦር ሀይል አዛዥ በምርጫው መወዳደር እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል፡፡ ይህም የሞርሲን ደጋፊዎች እና የጦር ሃይሉን ፍጥጫ የሚያባብሰው ሲሆን የግብፅን ሰላምና መረጋጋትም በጥርጣሬ የተሞላ እንደሚያደርገው የሚናገሩት ብዙዎች ናቸው፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

         የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ 572 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን ያፀደቀ ሲሆን ከዚህ ቀደም የወጡት ደረጃዎችም በአግባቡ እየተተገበሩ ስላልሆነ የማስፈፀም ሃላፊነት ያለበት ንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታችን እንዲወጡ ኤጀንሲው ጠይቋል፡፡ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ 10ሺህ ያህል ደረጃዎች ለማፅደቅ ቃል የገባው ኤጀንሲው ለብሄራዊ የደረጃዎች ምክር ቤቱ 631 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን አቅርቦ 572 ሲፀድቁ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽንን በተመለከተ ሊቀርብ የነበረውን ጨምሮ 59 ደረጃዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለጊዜው እንዲዘገዩ መደረጉን የኤጀንሲው የደረጃዎች ዝግጅት ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ለገሰ ገብሬ ከትላንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል፡፡ /በሰዎች ጤና እና አካል ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ምርቶችን በተመለከተ የሚወጡ ደረጃዎችን በማስፈፀም ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን የገለፁት ሃላፊው፤ ንግድ ሚኒስቴር ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በየዘርፉ የሚቀርቡ ደረጃዎች ሲገመገሙ ሰብሳቢ የሚሆነው የየዘርፉ አመራር መሆን አለበት የሚል አሰራር በመኖሩ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽንን በተመለከተ የቀረበው ደረጃ ያልፀደቀው ተወካዩ ባለመገኘታቸው መሆኑን የስራ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡ ብሄራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ጥር 7 ቀን 2006 ዓ.ም 11ኛ መደበኛ ስብሰባውን አድርጎ ካፀደቃቸው ደረጃዎች ውስጥ 309 አዲስ ሲሆኑ 33 የተከለሱ እንዲሁም 230 ነባር ደረጃዎችን ፈትሾ በማስቀጠል የፀደቁ መሆናቸውን አቶ ለገሰ ገልፀዋል፡፡ በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ውጤቶች የደረጃ ዝግጅት ዘርፍ 131 ደረጃዎች፣ በኮንስትራክሽንና ሲቪል ኢንጂነሪንግ 211 የኢትዮጵያ ደረጃዎች፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል የደረጃ ዝግጅት ዘርፍ 121 ደረጃዎች እንዲሁም በጤና፣በአካባቢና ደህንነት የደረጃ ዝግጅት ዘርፍ 109 የኢትዮጵያ ደረጃዎች የፀደቁ ሲሆን ደረጃዎቹን የሚመለከታቸው አካላት ተከታትለው የሚያስፈፅሙ ከሆነ፣ በአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው የተጠቀሰ ሲሆን የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን የሃገሪቱ ምርቶች በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላሉም ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ የአለማቀፉ የመስፈርት ተቋም (ISO) ሰርተፍኬትን ማግኘቱ ኤጀንሲው የሚሰጣቸው ደረጃዎች በአለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሚናው የላቀ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

በውድቅት ሌሊት “ዎክ” ማድረግ ያምረኝ ነበር
የሚዳቋ ጥብስ አምሮኝ ከየት ይምጣ?!

“እርግዝናው የመጀመሪያዬ ነው፡፡ በፊት በፊት ሴቶች ሲያረግዙ የማይሆን ነገር ያምራቸዋል ሲባል ስሰማ ሲሞላቀቁ ነው

እያልኩ አስብ ነበር፡፡ ግን ተሳስቻለሁ፡፡ ከእርግዝናዬ 3 ወራት በኋላ ውስጤ የሚፈልገውና የሚያምረኝ ሁሉ ግራ

የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ ደግሞ የፈለግሁትን ካላገኘሁ ፈጽሞ ጤና አይኖረኝም፡፡ ባለቤቴ ፍላጎቴንና አምሮቴን ለማሟላት

ከፍተኛ ጥረት በያደርግም አንዳንዴ አማረኝ የምለው ነገር እንኳን ለእሱ ለእኔም ግራ ይሆንብኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን

የጠየቅሁትን ፈልጎ ከማምጣት አይቦዝንም፡፡
“በቅርቡ ያጋጠመኝን ልንገርሽ፡፡ ጠዋት ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ የሚዳቋ ሥጋ ጥብስ አማረኝ አልኩት፡፡ የሚዳቋ ሥጋ

ከየት ይገኛል የበግ ወይ የፍየል ሥጋ ይገዛና ይጠበስልሽ አለኝ። በፍፁም አልፈልግም አልኩት፡፡ ለአንድ ጓደኛው ደወለና

ሲያማክረው ቻይና ሬስቶራንት ይዘሃት ሒድ አለው። ይዞኝ ሄደ፡፡ እኔ እራሴ በህይወቴ ሚዳቋ የምትባል ፍጡር አይቼ

አላውቅም፡፡ ምግቡ መኖሩን ስንጠይቅ አለ ተባልንና አዘዝን። የቀረበልኝን ምግብ አይነቱንም ሆነ አቀራረቡን ከዚህ

ቀደም አይቼው አላውቅም፡፡ ግን ጥርግ አድርጌ ነው የበላሁት። በጣም የገረመኝ ነገር ደግሞ ለቀረበልን አንድ የምግብ

የከፈልነው ከ800 ብር በላይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ምግብ ዳግም እንዳያምርኝ ፀሎቴ ነው፡፡”
በጳውሎስ ሆስፒታል ለእርግዝና ክትትል መጥተው ካገኘኋቸው ነፍሰጡር ሴቶች መካከል የስምንት ወር ነፍሰጡሯ

ሰናይት ታከለ ነበረች ከላይ የቀረበውን ታሪክ የነበረችኝ፡፡ በሆስፒታሉ አግኝቼ ካነጋገርኳቸው ነፍሰጡር ሴቶች መካከል

አብዛኛዎቹ በእርግዝና ወቅት የተለያዩ ነገሮች አምሮት በተለያየ ጊዜ እንደሚያጋጥማቸውና ያማረቸውን ነገር ካላገኙ

ወይም ካልበሉ ጤናቸው እንደሚጓደል ይገልፃሉ፡፡
አንድ ልጅ ወልዳ ሁለተኛውን ለመውለድ እየተጠባበቀች የምትገኘው ሠላም ፍቃዱ፤  በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው

አምሮት ጉዳይ ከመጀመሪያ እርግዝናዋ በኋላ እንዳላስቸገራት ትናገራለች፡፡ “የመጀመሪያ ልጄን እርጉዝ ሆኜ የብዙ ነገሮች

አምሮት ያሰቃየኝ ነበር፡፡ እኔ በአብዛኛው የሚያምረኝ የሚበሉ ወይም የሚጠጡ ነገሮች አልነበረም፡፡ በውድቅት ሌሊት

ተነስቼ በባዶ እግሬ ወክ ማድረግ በጣም ያምረኝ ነበር፡፡ ባለቤቴ ደግሞ ይሄንን አይፈቅድልኝም፡፡ የሲጋራ ጭስና

የተበላሹ ምግቦች ሽታም ወልጄ እስክገላገል ድረስ በየዕለቱ ውል እያሉ ያስቸግሩኝ ነበር፡፡ ይህ አምሮቴ ባለቤቴ የአጫሽ

ጓደኛውን በሲጋራ ጭስ የታጠነ የአንገት ሻርፕ ለማምጣት እስኪገደድ አድርሶት ነበር፡፡
“አሁን ሁለተኛ ልጄን ሳረግዝ ግን ያ ሁሉ ስሜትና ፍላጎት ጠፍቷል፡፡ ምንም ችግር ሳያምረኝ ነው ዘጠኝ ወሬን

የጨረስኩት፡፡ አሁን ለመውለድ የቀረኝ ጥቂት ቀናት ነው፡፡ በዚህ ጊዜም የተለየ አምሮት ያጋጥመኛል ብዬ አላስብም”

ብላለች፡፡
“ባለቤቴ በነፍሰጡርነት ያሳለፈቻቸው ጊዜያት ለእኔ የፈተናና የሥቃይ ወራት ነበሩ፡፡ የባህርይዋ መለዋወጥ፣ የፍላጎቷ

መብዛት፤ ተነጫናጭነቱ ምርር አድርገውኝ ነበር፡፡ “ምነው ባይወለድ ቢቀርስ” እስክል ድረስ ነው የተማረርኩት፡፡ ሌሊት

እንቅልፍ የሚባል ነገር የላትም፡፡ የበላችው ነገር ፈፅሞ አይረጋላትም፡፡ አንዳንዴ ስቃይዋ በጣም ያሣዝነኝ ነበር፡፡

ፍላጐቷን ለማሟላትና የምትጠይቀኝን ሁሉ ለመፈፀም ጥረት ባደርግም ደስተኛ አትሆንም። ይህ ደግሞ እኔን በጣም

ያናድደኝ ነበር፤ ኡይ ያ የፈተና ወቅት ነበር፡፡ አማረኛ ያለችውን ነገር ለማግኘት ብዙ መከራ አይቼ ፈልጌ ሳመጣላት

“አሁን አምሮቴ አለፈልኝ፣ አልፈልገውም” ብላ ወሽመጤን ብጥስ ታደርገዋለች፡፡ አንድ ጊዜ የኔ ቢጤ ፍርፋሪ

ከነመያዣው (አቁማዳ ነው መሰለኝ የሚባለው) አማረኝ ብላ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ሄጄ፣ ከኔ ብጤዎች ላይ ገዝቼ

ሳመጣላት፣ “አሁን አለፈልኝ አልፈልግም” አለችኝ፤ እኔ እሱን ለማግኘት የከፈልኩት መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም፡፡ ግን

ምን ታደርጊዋለሽ፡፡ የሚስቶች የእርግዝና ወቅት የባሎች የፈተና ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በድጋሚ እንድታረግዝ

አልፈልግም፡፡” በሚስቱ የነፍሰጡርነት አምሮት የተማረረ አባወራ ያጫወተኝ ነበር፡፡
ነፍሰጡርነት ለሔዋኖች ብቻ የተሰጠ፣ ዘርን የመተካት ተፈጥሮአዊ ሒደትና ፀጋ ነው፡፡ እርግዝና ከ15-45 የዕድሜ ክልል

ውስጥ ባሉ ሴቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን በአማካይ የሰው ልጅ የእርግዝና ወቅት 40 ሣምንታት ወይም 280 ቀናትን

ይፈጃል። በእርግዝና ወራት ሰውነት የተለያዩ ለውጦችን ያስተናግዳል፡፡
ነፍሰጡር ሴት በእርግዝናዋ ሳቢያ የተለያዩ ሆርሞኖች በሰውነቷ ውስጥ ይፈጠራሉ፡፡ እነዚህ ሆርሞኖችም በሰውነቷ

የተለያዩ ክፍሎች ላይ የሚታዩ ለውጦችን ያስከትላሉ፡፡ በባህርይዋ፣ በአተነፋፈሷ፣ በልብ ምቷ ና በምግብ ፍላጎቷ ላይ

ለውጥ ይከተላል፡፡
የባሎች ትዕግስትና የፍቅራቸው ልክ ከሚፈተኑባቸው አጋጣሚዎች መካከል የሚስቶቻቸው የእርግዝና ወቅት ተጠቃሽ

ነው። በእርግዝናዋ የመጀመሪያ 3 ወራት ማስመለስና ማቅለሽለሽ በብዛት ሊያጋጥማት ይችላል፡፡ የምግብ ፍላጎቷና

ምርጫዋ የተለየ ሊሆንም ይችላል፡፡ ነፍሰጡር ሴቶች በእርግዝና ወቅት የተለያዩ ነገሮች እንዲሚያምሯቸው ሲናገሩ

ይሰማል:- አፈር፣ የመኪና ወይም የሲጋራ ጭስ፣ የቤንዝን ወይም የተበላሸ ምግብ ሽታ፣ ሣሙና፣ ሊጥ፣ ትርፍራፊ

ምግቦች፣ የኮመጠጡ መጠጦች፣ ያምረናል ከሚሏቸው ነገሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በእርግዝና ወቅት ለሚከሰት የተለየ የምግብ አምሮት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች እንዳሉ

የሚናገሩት የማህፀንና ፅንስ ሃኪሙ ዶክተር አክሊሉ ወንድሙ፤ ከእነዚህ አንዱ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የብረት

ማዕድን እጥረት መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
በዚህ ማዕድን እጥረት የተነሳ የደም ማነስ የሚፈጠርባቸው ነፍሰጡር ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት የማይበሉ ነገሮችና

ለመብላት የመፈለግ ባህርይ ሊያሣዩ ይችላሉ፡፡ እንደአገራችን ባሉ ታዳጊ አገራት ከ48 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሴቶች

የብረት ማዕድን እጥረት ይታይባቸዋል ያሉት ዶክተሩ፤ “ለዚህም ምክንያቱ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና፣ አከታትሎ

መውለድና በወሊድ ወቅት የሚያጋጥም የደም መፍሰስ ሊሆኑ ይችላሉ። በእነዚህ ምክንያቶች የብረት ማዕድን እጥረት

የገጠማት ሴት በእርግዝናዋ ወቅት እንደ አፈር፣ ሣሙና፣ ትርፍራፊ ምግቦችና መሰል ያልተለመዱ ነገሮችን የመብላት

ፍላጐትና አምሮት ይኖራታል፤ እነዚህ የማይበሉ ነገሮች ደግሞ ንፅህና የሌላቸውና ለምግብነት የሚዘጋጁ ባለመሆናቸው

በነፍሰጡሯ ላይ እጅግ አደገኛ የሆኑ የጤና ችግሮችን ሊያስከትሉባት ይችላሉ” ሲሉ አስረድተዋል። የማይበሉ ነገሮች

የሚያምራቸውና የሚበሉ ነፍሰጡር ሴቶች፤ ምናልባትም የሥነ አዕምሮ ችግር ያለባቸው ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል -

ዶክተር አክሊሉ። ሌላው ጤናማ የሚባለውና እርግዝናን ተከትሎ በሴቷ ሰውነት ላይ በሚፈጠር የሆርሞን ለውጥ ሣቢያ

በበርካታ ሴቶች ላይ የሚከሰት አምሮት ነው። የሆርሞን ለውጡ ከነርቭ ሥርዓት ሒደት ጋር በተያያዘ የምግብ ፍላጐትና

ምርጫ ላይ ለውጥ ይፈጥራል፡፡ ነፍሰጡሯ ሴት የምትመገበው ምግብ፣ በሆዷ ለያዘችው ፅንስ ጭምር በመሆኑ ምግቡን

የሚጋራት አካል በውስጧ ስለአለ ሰውነቷ የምግብ እጥረት ያጋጥመዋል፡፡ በዚህ ወቅትም በአንድ የተለየ ወይም የተወሰነ

ምግብ ላይ ትኩረት እንድታደርግ ያስገድዳታል፡፡
“ይህ ጤናማ የእርግዝና አምሮት ሊባል ይችላል” ያሉት ዶክተር አክሊሉ፤ ነፍሰጡሯ ምንም ያህል ፍላጐትና አምሮት

ቢኖራት ንጽህናቸው ያልተጠበቁ ምግቦችን ወይም ለምግብነት የማይውሉ ነገሮችን በምንም ዓይነት ሁኔታ መመገብ

እንደሌለባት አበክረው አስገንዝበዋል፡፡ በእርግዝና ወቅት የሲጋራ ወይንም የቤንዝን ሽታ አማረኝ የሚሉ ሴቶች ወይንም

አምሮቱ የሚያጋጥማቸው ነፍሰጡሮች በተቻላቸው መጠን አምሮታቸውን ለመርሳትና በሌሎች ነገሮች ለመለወጥ ጥረት

ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን በማድረጋቸው ምክንያትም በእነሱም ሆነ በማህፀናቸው ባለው ፅንስ ላይ የሚፈጠር

ችግር አይኖርም ሲሉም ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡ በአምሮት ሰበብ ለእናቲቱም ሆነ ለጽንሱ እጅግ አደገኛ የሆኑ ነገሮችን

ከማድረግም መቆጠብ እንደሚገባ ዶክተር አክሊሉ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ጤናማና ንቁ ልጅ ወልዶ ለመሳምና የእርግዝና

ወራትን በሰላም ለማጠናቀቅ፣ ይቻል ዘንድ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥሙትን የተለያዩ አዕምሮቶችን በብልሃትና

በጥንቃቄ ማለፍ እንዳለባቸው ነፍሰጡር ሴቶች ሁሉ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ 

Published in ዋናው ጤና

ከደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ወደ የሚገኘው የኦሊቨርታምቦ አየር ማረፊያ የደረስነው ባለፈው ሃሙስ 9 ሰዓት አካባቢ ነበር፡፡ በበደሌ ስፔሻል የጉዟችን ሙሉ ወጭ ተሸፍኖ የቻን ውድድርን ለመዘገብ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናነው ጋዜጠኞች ከላይ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማልያ ለብሻለሁ፡፡ ከውስጥ የለበስኩት ቲሸርት ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ማልያ ነው፡፡ የመግቢያ ቪዛዬን የመረመረው የኢምግሬሽን መኮንን አለባበሴን ሲያይ ዝም ማለት አልቻለም፡፡ ለምን ማሊያ እንዳቀላቀልኩ ሲጠይቀኝ፤ የሁለቱም አገራት ደጋፊ ነኝ አልኩት፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ ማጣርያው ካልቀናትና ከተሰናበተች፤ በሁለተኛ ደረጃ የምደግፈው አገር ደቡብ አፍሪካ ነው አልኩት፡፡

የኢምግሬሽን መኮንኑ ፓስፖርቴን እየመረመረ ደቡብ አፍሪካ ናይጄርያን ካሸነፈች ለዋንጫ ትደርሳለች አለኝ፡፡ እኔም፤ ኢትዮጵያ በሁለተኛው ጨዋታዋ ኮንጎ ብራዛቪልን ካሸነፈች ከምድብ የማለፍ እድል ይኖራታል አልኩት፡፡ የመልካም እድል ምኞት ተለዋውጠን ተለያየን፡፡ የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ ወሳኝ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ትናንት እና ዛሬ ነበር የተደረጉት፡፡ ዋልያዎቹ በምድብ የመክፈቻ ጨዋታ በደረሰባቸው የ2ለ0 ሽንፈት ምክንያት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መከፈታቸውን ለመረዳት ብዙ አያስቸግርም፡፡ በዋና ከተማዋ ጆሃንስበርግ ውስጥ፣ ጄፒ ስትሪት አካባቢ የሚገኘው የጆበርግ መርካቶ ላይ ያጠላውን ድባብ መመልከት ብቻ ይበቃል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በንግድ ስራ ተሰማርተው የሚንቀሳቀሱበት እና ከተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ግዛቶች በመምጣት እንደ መናሐርያ የሚገናኙበት የጆበርግ መርካቶ፤ ባለፈው ሃሙስ ከ10 ሰዓት በኋላ እንደልማዱ ጭር ሲል በአካባቢው ተዘዋውሬ የተመለከትኩት ሁኔታ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል፡፡ ባለሸንተረሩን፤ ወይንም ቢጫውን ካልሆነም አረንጓዴውን የዋልያዎቹ ማልያ የለበሰ ኢትዮጵያዊ እንደ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ሰሞን አልነበረም፡፡ እንደውም በጆበርግ መርካቶ አካባቢ የሚታየው ከብሄራዊ ቡድን ጋር የተያያዘ ድባብ የዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ርዝራዥ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህን የዋልያዎቹ ማልያ በጆሃንስበርግ እስከ 140ራንድ መሸጡን ያሰታወሰው አንድ ነጋዴ ሰሞኑን በከተማዋ ለኢትዮጵያ እና ለደጋጋፊዎቿ ሲሸጥ የነበረው ማልያ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለገበያ ቀርቦ ከነበረው የተረፈ መሆኑን ይናገራል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በ2010 እኤአ ላይ በዚያው አገር በተካሄደው19ኛው ዓለም ዋንጫ ወቅት ለውድድሩ ትኩረት የነበረውን የቩቩዜላ ጥሩንባ በማምረት እና በመቸርቸር እንዲሁም በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ 32 ብሄራዊ ቡድኖች ማልያ በመሸጥ ከፍተኛ ገበያ ነበራቸው፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ መሳተፏን በድምቀት ያከበሩት እነዚህ ኢትዮጵያውን፤ በወቅቱ የዋልያን ማልያ በደቡብ አፍሪካ ስታድዬሞች በተለይም ብሄራዊ ቡድኑ በተጫወተባቸው ሁለት ከተሞች ሩስተንበርግ እና ኔልስፕሪት እንዲሁም በመናሐሪያቸው ጆሃንስበርግ ከተማ በመቸብቸብ እና በመልበስ የማልያውን ተወዳጅነት ጨምረውታል፡፡ ይሄው በደቡብ አፍሪካ ተመርቶ እና ለገበያ የቀረበው የዋሊያዎቹ ማልያ፤ ወደ ኢትዮጵያ፤ ወደ ሰሜን አሜሪካ እና ወደ አውሮፓ ተልኮም ከፍተኛ ገበያ እንዳገኘ ተገልጿል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ሰኞ እለት ዋልያዎቹ ከሊቢያ አቻዎቻቸው ጋር ባደረጉት ጨዋታ የገጠማቸው የ2ለ0 ሽንፈት ያበሳጫቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪካ ሲገባ ያደረግነው አቀባበል ከአፍሪካ ዋንጫው በተለየ የደመቀ ነበር ያለው ብሩክ የተባለ ወጣት፤ ያን ጊዜ እንበላዋለን ብለን ጨፈርን፤ አሁን ለቻን ሲመጡ ደግሞ ሁላችንም እናስብ የነበረው በሊቢያ እንዲሸነፉ ሳይሆን ለዋንጫ እንዲደርሱ ነው ብሏል፡፡ ያነጋገርኳቸው የጆሃን ስበርግ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በቻን የመክፈቻ ጨዋታ ዋልያዎቹ የነበራቸውን ብቃት አንገት ያስደፋል ብለው ገልፀውታል፡፡ አንዱ ወጣት ነጋዴ እንደውም ቡድኑ ከሊቢያ ጋር ባደረገው ጨዋታ የነበረው ሁኔታ ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራን ያስመስለው ነበር ብሏል፡፡ ለሰላሣ አመታት ርቆን ስንመኘው ወደነበረው የአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ለመግባት መብቃታችን ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ዋሊያዎቹ ለአህጉሪቱን የእግር ኳስ ዋንጫ ከሚፎካከሩ 16 ቡድኖች መካከል አንዱ ለመሆን በመቻላቸው የህዝቡ ስሜት የቱን ያህል እንደተጠቀለለ አይተናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

ነገሩ ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል አይደለም፡፡ በእንግድነት የረገጥነው አህጉራዊ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ቤተኛ እየሆንን ነው፡፡ አለም ዋንጫ ማጣሪያ እስከ መጨረሻው ዙር በስኬት በመጓዝ ከአስሩ ቡድኖች መካከል አንዱ ለመሆን ችለናል፡፡ በዚህም አላበቃም፡፡ በአህጉራዊው የቻን ውድድር ውስጥ ገብተናል፡፡ አሁን ተራ ነገር ቢመስልም ለብዙ አመታት ስንናፍቀው የነበረ ነው አህጉራዊው የእግር ኳስ መድረክ፡፡ ነገር ግን ባዕድ ሆኖብን በነበረው መድረክ ላይ ቤተኛ እየሆንን ብንመጣም በቂ አይደለም፡፡ በአህጉራዊው መድረክ ጠንካራ ተፎካካሪና አሸናፊ የመሆን ምኞታችን ገና አልተነካም፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ባለፈው 2 ዓመት ውስጥ ካደረጋቸው ጨዋታዎች አንዱንም አላሸነፈም፡፡ ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ ጋር 1ለ1 አቻ ከወጡ በኋላ ፤ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከዛምቢያ ጋር አንድ ለአንድ አቻ፤ በቡርኪናፋሶ 4ለ0 እና በናይጄርያ 2ለ0 በሆነ ውጤት ሁለት ሽንፈት አስተናግደው ከውድድሩ ውጭ ሆነዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ቡድኑ ከዚህ ልምዱ ተነስቶ በቻን ውድድር የተሻለ ውጤት ያስመዘግባል የሚል ከፍተኛ እምነት ነበራቸው፡፡ - እስካሁን አልተሳካም እንጂ፡፡

በሊቢያው ጨዋታ አንዳንድ ደጋፊዎች አምበሉን ደጉ ደበበን ተበሳጭተውበት እንደነበር የገለፀው ታሪኩ የተባለ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ፤ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የተጫዋቹን ወቅታዊ አቋም በመረዳት ማሰለፍ እንዳልነበረበት እና በሱ ምትክ ሳላዲን በርጌቾን በማጫወት በቡድኑ ላይ የደረሰውን ሽንፈት እና በተጨዋቹ ላይ ያለ አግባብ የተፈጠረውን ትችት መከላከል ይችል ነበር ብሏል፡፡ ብሩክ የተባለው ኢትዮጵያዊ የደቡብ አፍሪካ ነዋሪ በበኩሉ በጨዋታው ላይ አዳነ ግርማ ከፍተኛ ድካም የገጠመው ያለቦታው በመሰለፉ ነው የሚለው ኢትዮጵያዊው ብሩክ፤ ከሜዳ ውጭ ረዳት አሰልጣኝ እና ሌሎች የቡድኑ አባላት እንዲህ አድርግ እዚያ ጋር ሸፍን በሚል በሚያዥጐደጉዱበት ትዕዛዝም ያደክማል በማለት ወቅሷል፡፡ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ከሃዘናቸው ባሻገር ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ወደፊት ብሄራዊ ቡድኑ በስብስቡ በወጣት ተጨዋቾች ተጠናክሮ ውጤት እንደሚያገኝ ስለሚያምኑ በደስታ መደገፋቸውን እንደማያቋርጡ ይገልጻሉ፡፡ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን እንደገለፁት የሊቢያውን ጨዋታ ለመመልከት ስራቸውን ትተው ከተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ወደ ፍሪስቴት ስታድዬም በመጓዝ ጨዋታውን የታደሙ ቢሆንም በዋልያዎቹ ያስመዘገቡት ውጤት አሳዝኖቸዋል፡፡ በምድብ 3 የተደለደሉት ዋልያዎቹ የመክፈቻ ጨዋታቸውን በፍሪ ስቴት ስቴድዬም ሲያደርጉ፤ ድጋፋችንን ለመስጠት እስከ 10 አውቶብስ ያህል ሆነን መጥተናል ብሏል - በደቡብ አፍሪካ አምስት አመት የሆነው ኢትዮጵያዊ በአጠቃላይ ለጨዋታው እስከ 8ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ስታድዬም መግባታቸውን፤ የገለፀው ይሄው ኢትዮጵያዊ፤ የትኬት ዋጋ ከ50 እስከ 70 ራንድ መክፈላቸውን ተናግሯል፡፡ ከ100 እስከ 140 ብር ገደማ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ድጋፍ የደቡብ አፍሪካ የፀጥታ ሃይሎች ሳይቀሩ ተደስተዋል፡፡ የቻን ውድድር ድምቀት እናንተው ናችሁ በማለት የፀጥታ ጥበቃ ሃይሎች ኢትዮጵያውያን ሲያበረታቱ እንደነበሩና እንዳይ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው እና በነፃ ስታድዬምም እንዲገቡ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡድን በመሸነፉ የብዙዎቹ ስሜት ቢቀዘቅዝም ተስፋ ሳይቆርጡ ሁለተኛውን ጨዋታ ለመመልከት መጠባበቃቸው አልቀረም፡፡ እስከመጨረሻው ድረስ ድጋፍ መስጠታቸውም አያጠራጥርም፡፡ ዋልያዎቹ ኮንጎ ብራዛቪልን ማሸነፍ ከቻሉ ግን፤ የኢትዮጵያውያኑ ደጋፊዎች ስሜት እንደገና ይሟሟቃሉ፡፡

ዋሊያዎቹ የፊታችን ሰኞ የምድባቸውን የመጨረሻ ጨዋታ ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር ሲያደርጉ በርካታ ደጋፊዎች ስታድዬም እንደሚገቡም ይገመታል፡፡ ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላይ የነበረውን ጉዞ በንቃት መከታተላቸውን የሚናገሩት ኢትዮጵያውያን፤ ዋልያዎቹ ደቡብ አፍሪካን በሜዳቸው ሁለት ለአንድ ባሸነፉበት ጊዜ በጆሃንስበርግ መርካቶ የነበረው ደስታ ወደር እንዳልነበረው ያስታውሳሉ፡፡ እዚህ በሰው አገር ከደስታችን ብዛት መንገድ ሁሉ ተዘግቶ በጭፈራ ደምቆ እንደነበር፤ ደቡብ አፍሪካውያኑን በማብሸቅ ከፍተኛ ድራማ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ታልፋለች በሚል ተስፋ ከናይጄርያ ጋር የተደረጉ የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን እንደተከታተሉ ገልፀው፤ ኢትዮጵያ በመጀመርያው ጨዋታ በሜዳዋ መሸነፏን ሲያዩ ማዘናቸውንና የካላባሩ ጨዋታ ብዙም እንዳልሳባቸው ተናግረዋል፡፡ ሐሙስ እለት በጆሃንስበርግ ከተማ በሚገኘው እና ኢስትጌት በተባለው የገበያ ማዕከል ስንዘዋወር ቆይተን አንድ የስፖርት ትጥቆች ሱቅ ውስጥ ገባን፡፡

የተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ማልያዎች እየተመለከትኩ በነበረበት ጊዜ ነው አረንጓዴ ቱታ የለበሱ ተጨዋቾች ወደሱቁ የገቡት፡፡ የኮንጎው ብራዛቪል ክለብ ኤሲ ሊዮፓርድስ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ አንዱን ወጣት ተጨዋች ንናግረው ስሞክር እኔ በእንግሊዝኛ እሱ በፈረንሳይኛ አልተግባባንም፡፡ በሬዲዮ የስፖርት 365 አዘጋጅና በኢንተርስፖርት ጋዜጣ ማኔጂንግ ዲያሬክተር ሁሴን አብዱልቀኒ ነው በፈረንሳይኛ ያግባባን፡፡ ኤሲ ሊዮፓርድስ በኮንጎ ብራዛቪል ትልቅ ክለብ እንደሆነ ወጣቱ ተጫዋች ገልፆ፤ በክለቡ የወጣቶች አካዳሚ ውስጥ እግር ኳስን ሰልጥኖ ዋናውን ቡድን በ21 ዓመቱ እንደተቀላቀለ ነገረኝ፡፡ ለኮንጎ ብሄራዊ ቡድን ባለመመረጡ ቢያዝንም፤ ውድድሩን በጉጉት እየተከታተለው ነው፡፡ ከምድብ 3 የሚያልፉት እነማን ይሆናሉ ተብሎ ሲጠየቅ በሰጠን መልስ፤ ኢትዮጵያ እና ሊቢያ ጠንካራ ቡድኖች በመሆናቸው ከጋና ይልቅ እንፈራቸዋለን ብሏል፡፡ የኤሲ ሊዮፓርድሱ ተጨዋች ለስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ መጫወት እንደሚፈልግ ሲነግረኝ፤ የሚያስደንቅ ህልም አለህ ብዬ እንደሚያሳካው በመመኘት ተሰናበትኩት፡፡

“...በአሁን ወቅት ዕድሜው 22 ዓመት ነው። የወሲብ ጥቃቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈፀመበት ግን የ10 ዓመት ልጅ በነበረ

ጊዜ ነው፡፡ የዚህ ታሪክ ባለቤት የሆነው ህጻን ሁለቱም ወላጆቹ በህይወት አሉ፤ በጣም ጥሩ የገቢ ምንጭ ያላቸውና

በተለምዶ ሃብታም ቤተሰብ የሚባሉ የአዲስ አበባ ኗሪ ናቸው፡፡ ሆኖም ወላጆቹ ወደ ንግድ ሥራቸው እንጂ ከልጁ ጋር

የቅርብ ክትትልና በግልፅ የመነጋገር ልምድ አልነበራቸውም፡፡ የ10 ዓመት ህፃን እያለ አንድ ወንድ አስጠኚ ተመድቦለት

እቤት ውስጥ ሁለቱንም ብቻቸውን በመተው ወላጆቹ ወደ ሥራ ይሄዱ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር አስጠኚው የወሲብ ጥቃት

በህፃኑ ላይ የፈፀመበት፤ ይህ ድርጊት ተጠቂው 15 ዓመት እስኪሆነው ድረስ ቢቀጥልም ወላጆች ምንም የሚያውቁት ነገር

አልነበረም፡፡ ለአምስት ዓመታት ጥቃት ከፈፀመበት በኋላ ጥቃት ፈፃሚው አሜሪካን ሃገር ሄዷል፡፡ ጥቃት የተፈፀመበት

ልጅ ድርጊቱ ጥቃት መሆኑን ዘግይቶ ተረድቷል፤ ውስጡ የብቀላ ስሜት አድሮበታል፤ ቤተሰቦቹን ደጋግሞ ቢረግምም

የደረሰበትን ጉዳት በሚመለከት ምንም አልገለፀላቸውም፤ ራሱን እንደ ወራዳ፤ ቆሻሻ በመቁጠር የህይወት ትርጉም እንዳጣ

ገልጧል፡፡ አንዳንዴ ራሱን የማጥፋት ስሜት ይሰማዋል፡፡
በላይ ሓጎስ አዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ሓምሌ 27 ቀን 2002 ዓ.ም.
ከላይ ያነበባችሁትን መረጃ ያገኘነው ከበላይ ሐጎስ ጥናት ነው፡፡ ይህን አምድ በዚህ ጥናት መነሻነት መረጃ ያቀረብንበት

ምክንያትም የተለያዩ አንባቢዎች ከአሁን ቀደም ለንባብ ቀርበው የነበሩ ጽሁፎችን መነሻ በማድረግ ያቀረቡዋቸውን

ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለንባብ ቀርቦ የነበረው ሴት ህጻናት በወሲብ ጥቃት በሚደርስባቸው ጊዜ

በአንድ የህክምና ተቋም ውስጥ በሚቋቋም ማእከል የህክምና የፍትህ እና ስነልቡና አገልግሎት እንደሚሰጣቸውና

ባለጉዳዮቹ መንገላታት ሳይደርስባቸው ጥቃት አድራሹ ወደ ህግ የሚቀርብበት አሰራር ከአንድ አመት ወዲህ እንደተ

ጀመረ ይገልጸል፡፡ ሆኖም ግን ወንድ ልጆችን በሚመለከት ይህ አሰራር የሌለ ሲሆን ወንዶች የወሲብ ጥቃት

ቢደርስባቸው ሊታከሙ የሚችሉት በጠቅላላ ሐኪም ወይንም በቀዶ ሕክምና ባለሙያ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከዚህም

በመነሳት አንዳንድ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፡፡ ከጥያቁዎቹም መካከል...
የወንዶች ልጆች የወሲብ ጥቃት ምን ያህል አሳሰቢ ነው?
ወንድ ልጄ ተገዶ በመደፈሩ በእርግጥ ሕክምናውን አግኝቶአል፡፡ ነገር ግን እስከአሁን ድረስ መንፈሱ ትክክል አይደለም።

ለምንድነው?
ለምን ለወንዶቹስ እንደሴቶቹ የተለየ ተቋም አይዘጋጅላቸውም? የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ጥያቄዎቹ የሚጠቁሙዋቸውን ነጥቦች በትክክል መልስ ባይሰጥም ነገር ግን የበላይ ሐጎስ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) የዳሰሳ

ቅኝት ስለሁኔታው ያነሳቸውን ጠቃሚ ሀሳቦች ለአንባቢ ብለናል፡፡
ከፖሊስ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለከተው በአስሩም ክፍለ ከተሞች የህፃናት እንክብካቤ ማዕከላት በ1996 ዓ.ም.

የወሲብ ጥቃት ደርሶባቸው ጉዳያቸው ለፖሊስ ሪፖርት የተደረገ 47 ወንድ ህፃናት ዝርዝር መረጃ ተተንትኗል፡፡

በተጨማሪም በአንፕካን ኢትዮጵያ እርዳታ ሲያገኙ የነበሩት 13 የወሲብ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ወንድ ህፃናት መረጃንም

አካትቷል፡፡
የጥናቱ ግኝት ጥቃቱ የደረሰባቸው ወንድ ህፃናትን በሚመለከት የሚከተሉትን ነጥቦች በዝርዝር አስቀምጦአል፡፡
- በ1996 ዓ.ም. የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናት ጉዳይ ለፖሊስ ሪፖርት የተደረገው 218 ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ 47ቱ

ማለትም 22% በወንድ ህፃናት ላይ የደረሰ ነበር፡፡
- 51% የሚሆኑት ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናት ጉዳታቸውን ለፖሊስ እራሳችው ሪፖርት ያደረጉ ሲሆኑ፤ 34% ሪፖርት

የተደረገው በወላጆቻቸው ነበር፡፡ በአንፃሩ 3% ብቻ ነበር በፖሊስ ክትትል የታወቀው፡፡
- ይብዛም ይነስም በአስሩም ክፍለ ከተሞች በወንድ ህፃናት ላይ የወሲብ ጥቃት ተፈፅሟል፡፡
የጥቃቱ ሰለባ ወንድ ህፃናት ዕድሜአቸው ከ3-18 ዓመት ነበር፡፡ 77% የሚያህሉ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የደረሱ ተማሪዎች

ነበሩ፡፡
- አብዛኛው ማለትም 89% ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናት ከአልኮልና እፆች ልምድ ነፃ ነበሩ፡፡ ነገር ግን 6% የሚያህሉ  

የአልኮልና እፆች መጠቀም ልምድ ነበራቸው፡፡
- ጥቃቱ የደረሰባቸው በልዩ ልዩ ሰዎች ሲሆን 45% ያህሉ በጎረቤቶቻቸው፤ 36% በማይታወቁ ሰዎች፤ እንዲሁም 19%

በተለያዩ ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡
ከላይ የተገለጸው መረጃ በወንዶች ላይ የሚደርስ የወሲብ ጥቃት ምን ያህል አሳሳቢ ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ

ይሰጣል፡፡ ይህ ጥናት በተካሄደበት ጊዜ መረጃው የተሰበሰበው ከ1996 ዓ/ም ዶክመንት ሲሆን ከዚያ ወዲህ ያለውን

እውነታ ለማገናዘብ ይረዳል፡፡
ጥናቱ እንደሚጠቁመው ከተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎች የተሰበሰቡት አስተያየቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡  
ወሲባዊ ጥቃት በወንድ ህፃናት ላይ ይከሰታል ብሎ የሚገምት ኢትዮጵያዊ ወላጅ እስከቅርብ ጊዜ አልነበረም ለማለት

ያስደፍራል፡፡ ከዚህ ጥናት በኋላም ቢሆን አብዛኛው ወላጅም ሆነ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍል ምንም ግንዛቤ የሌለው

መሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
አንዲት እናት እንዳሉት የሴት ልጄን የወሲብ ጥቃት እንዳይደርስባት ከመስጋት ውጪ ወንድ ልጄ ለአፍታም ቢሆን

የወሲብ ጥቃት ይደርስበታል የሚል ጥርጣሬ አልነበረኝም ብለዋል፡፡
ይህ የብዙ ወላጅ ግምት ሲሆን በዚህ ጥናት የተዳሰሰው ግኝት ደግሞ ወላጆችንም ሆነ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን

ግምታቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያሳስብ ነው፡፡ ይላል የጥናት ወረቀቱ፡፡
ወንድ ህፃናት ለወሲብ ጥቃት ተጋላጭ የሚሆንባቸው ምክንያቶች፤
- ተጋላጭ አኗኗር
የቤተሰብ/የአሳዳጊ ትኩረት እና ክትትል ያለማግኘት፤
ከቤተሰብ ጋር በግልፅ የመወያየት ልምድ ያለመኖር፤
ተቀራርቦ መተኛት፤
ተገቢ መረጃ ያለማግኘት፤
በራስ የመተማመን ብቃት የሌለቸው ህፃናት፤
አሳዳጊና ተንከባካቢ የሌላቸው ህፃናት ...ወዘተ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በወንድ ህፃናት ላይ የደረሰው ወሲባዊ ጥቃት ያስከተለው ጉዳት፤
- አካላዊ ጉዳት፡-
የፊንጢጣ ማሳከክ፤
የአባለዘር በሽታ በአፍና በፊንጢጣ ላይ መገኘት፤
የብልት ማበጥ
- ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት፡
የወሲብ ህይወት ተበላሽቶብኛል ብሎ የመቆጨትና የመፀፀት፤
የወሲብ ስሜቴ ወደ ሴት ሳይሆን ወደ ወንድ ያደላብኛል ብሎ የመስጋት፤
ራስን ዝቅ የማድረግና ራስን የመጥላት ስሜት፤
ራስን የማጥፋት ስሜትና ሙከራ፤
ከተለመደው ሥፍራ የመጥፋት ስሜት እና ለመጥፋት መሞከር፤
የመፍራትና የመጨነቅ ስሜት፤ ኤችአይቪ ይዞኝ ይሆናል ብሎ መጨነቅ፤
በወንድ ህፃናት ላይ የብቀላ ስሜት፤
የመጣላትናት የመጋጨት ስሜት፤
ከእድሜው የማይጠበቅ የወሲብ ነክ አገላለፆችንና ድርጊቶችን መፈፀም፤
ከዚህም በተጨማሪ ጉዳቱ ማህበራዊና ስነልቡናዊ ቀውስን የሚያስከትል ሲሆን መገለጫዎቹም...
ማህበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ፡
ሰዎችን መጠራጠር ሰዎች ስለኔ ይወያያሉ /ያወራሉ ብሎ መገመት/ መጨነቅ፤ ሰዎች ያርቁኛል ብሎ መስጋት፤ ከሰዎች

መራቅ፤ መለየት፤ መገለል፤
በትምህርት ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ፡
ትምህርት ለመከታተል መቸገር፤ ትኩረት ማጣት፤ ከትምህርት መቅረት፤ ማቋረጥ፤ ምትመህርት ዝቅተኛ ውጤት

ማግኘት፤ ከክፍል ወደ ክፍል ለመዛወር መቸገር፤ ክፍል መድገም ከክፍል ጓደኞች ጋር ለመቀራረብ መቸገር...

የመሳሰሉትን ጉዳቶች ያስከትላል የበላይ ሐጎስ የጥናት ዳሰሳ እንደሚያስረዳው፡፡ 

Published in ላንተና ላንቺ
Saturday, 18 January 2014 00:00

ጥምቀት በአዲስ አበባ

ከ123 አብያተ ክርስትያን የሚወጡ ታቦታት በ46 ጥምቀተ ባሕሮች ያድራሉ

በየዓመቱ በኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በሀገሪቱ ውስጥ በጐዳናና በአደባባይ ከሚከናወኑ በዓላት አንዱ ነው፡፡ አንዲት የውጭ ሀገር ዜጋ በአንድ ዘመን ይህን በዓል ከተመለከተች በኋላ፤ “በየትኛውም ሀገር የሚከበር ካርኒቫል የማይተካከለው፣” ስትል አድንቃ ጽፋለች። ይቺ ጸሓፊ በብራዚል ዘመን መለወጫ ላይ የሚፈፀመውን ካርኒቫል ጭምር በመጥቀስ ነበር የጥምቀቱን አቻ የለሽነት የገለጠችው፡፡ አውሮጳዊቷ ጥምቀትን የተመለከተችው አዲስ አበባ ላይ ነበር፡፡ የጥምቀትን በዓል የደመቀና ቀለማም የሚያደርገው ከአከባበሩ ሥነሥርዓት ጋር በዓሉ የሚከናወንበት ቦታም የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። በከተማና በገጠር ያለው አከባበር ሥነ ሥርዓት አንድ ቢሆንም በድምቀቱ ይለያያል፡፡ ይህም ማለት በከተማ ውስጥ ብዙ ሕዝብና ብዙ ታቦታት በመኖራቸው ነው፡፡ “አርባ ዓራቱ ታቦት” የሚል የተሳሳተ ጥሪ የፈጠረው የጐንደሩ ጥምቀት፣ በነገሥታቱዋ ዘመን በጐንደር የነበሩት ፵፬ አድባራት በአንድነት ወጥተው፣ በነገሥታቱ የመዋኛ ቦታ ተሰብስበው እጅግ ልዩ ድምቀትና የበዙ ቀለሞችን ስለሚፈጥሩበት ነው፡፡ እንደዚህ ሲታይ ነው ጥምቀት በአዲስ አበባ እጅግ ልዩ ኾኖ የሚገኘው፡፡

በየትኛውም የሀገሪቱ ከተሞች ጥምቀት የሚከበረው በአንድ ቦታ ሲኾን በአዲስ አበባ ውስጥ ግን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ነው፡፡ የሚያስገርም ነው:- ጥምቀት አዲስ አበባ በሚባለው ክልል ውስጥ በ46 የጥምቀት ባሕሮች ላይ ይከበራል! በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ ከ120 በላይ የሚኾኑ አብያተ ክርስትያኖች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቤተክህነት ባገኘነው የዘንድሮ የጥምቀት በዓል አከባበር መርሐ ግብር ዝርዝር መሠረት፤ 123 አብያተ ክርስትያን ወደተለያዩ ቦታዎች ታቦታቶቻቸውን ይዘው ይወጣሉ፤ ይመለሳሉ፡፡ መንገዶች ኹሉ ወደ ጥምቀተ ባሕሮች በሚሔዱ፣ ከጥምቀተ ባሕሩም ወደየቤታቸው በሚመለሱ ታቦታት እና እነሱን አጅቦ በሚከተል ጥምቀትን አክባሪ ምዕመናን፣ ከከተራ ጀምሮ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ የተሞላ ይኾናል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎችም አራተኛ ቀኑን (ጥር 13) ይጨምራል፡፡ ከእያንዳንዱ ቤተክርስትያን በትንሹ ሁለት ታቦታት መውጣታቸው አይቀርም፡፡ በድምሩ ከሁለት መቶ ሃምሳ ያላነሱ ታቦታት፤ ዛሬ ጥር 10 ቀን ከየአድባራቱ በመውጣት ወደ 46ቱ ጥምቀተ ባሕሮች ይወርዳሉ፡፡

ከነዚህ የአዲስ አበባ ባሕረ ጥምቀቶች ውስጥ 15ቱ ብቻ ናቸው የአንድ አንድ ቤተክርስትያን ታቦቶች ማደሪያና ጥምቀትን ማክበሪያ የሚሆኑት። ሁለት ሁለት ቤተክርስትያኖች የሚያከብሩባቸው 12 ጥምቀተ ባሕሮች ያሉ ሲሆን፣ የሦስት ሦስት አብያተ ክርስትያን ታቦታት የሚያድሩባቸው ደግሞ 7 ባሕረ ጥምቀቶች ናቸው፡፡ በአምስት ባሕረ ጥምቀቶች አራት አራት ቤተክርስትያኖች እንደሚያድሩም ከቤተክሕነቱ ዝርዝር ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ስሌት፣ አምስት አምስት አብያተ ክርስትያናት ጥምቀትን የሚያከብሩባቸው አራት ባሕረጥምቀቶች ሲኖሩ፣ ከቀሩት ሦስት ባሕረ ጥምቀቶች ሁለቱ፤ ከስድስት እና ከሰባት አድባራት የሚወጡ፤ አንዱ ደግሞ ከአስር አድባራት በሚወጡ ታቦታትና ምዕመናን በድምቀት የሚከበርበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የጃንሜዳው ጥምቀተ ባሕር፣ ከዚህ በፊት የ11 አብያተ ክርስትያናት ጥምቀት ማክበሪያ እንደነበረ የሚታወቅ ቢኾንም፣ በዘንድሮው ዝርዝር ላይ ለማረጋገጥ የተቻለው በጥምቀተ ባሕሩ የሚያድሩት ከ10 አድባራት የሚወጡ ታቦታት እንደሆኑ ነው። ምናልባት እንደምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ያለውንም በመቁጠር ይሆናል 11 ሲባል የቆየው ያስብላል፡፡ ስደተኛው በመባል የሚታወቀው የምስካየኅዙናን መድኃኔዓለም ግን ለጥምቀትም ታቦቱ ከቤተክርስትያኑ የማይወጣበት ሥርዓት ካላቸው ገዳማት አንዱ ነው፡፡ በጃንሜዳው የሚያድሩ ታቦታት ከታዕካ ነገሥት በዓታ፣ ከመ/ጸ/ቅድስት ሥላሴ፣ ከገነተጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ፣ ከመንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም፣ ከቀጨኔ ደ/ሰ/መድኃኔዓለም፣ ከደ/ነ/ቅ/ዮሐንስ፣ ከመ/ል/ቅ/ማርቆስ፣ ከቀበና መ/ሕ/አ/ገ/መ/ቅዱስ፣ ከገነተ ኢየሱስ እና ከአንቀጸ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሚወጡ ታቦታት ናቸው፡፡ ከጃንሜዳው በመቀጠል ከሰባት አድባራት የሚወጡ ታቦታት፤ ጥምቀትን የሚያከብሩበት ጥምቀተ ባሕር ደግሞ በኮልፌ - ቀራንዮ፣ በትንሹ አቃቂ ወንዝ ላይ በሚገኘው ገዳመ ኢየሱስ ቅጽረ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ቦታ የቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ የደብረ ገሊላ ዓማኑኤል፣ የሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ፣ የገዳመ ኢየሱስ፣ የደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ፣ የወይብላ ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም እና የፊሊዶሮ አቡነተክለሃይማኖት ታቦታት ያድራሉ፡፡

በኮተቤው ወንድይራድ ት/ቤት አጠገብ በሚገኘው ጥምቀተ ባሕር ደግሞ ከ6 አድባራት የሚወጡ ታቦታት ያድራሉ፡፡ በጉለሌው የራስ ኃይሉ ሜዳ፣ በኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 24 ቀበሌ 15፣ በደብረ ዘይት መንገድ ፍሬሕይወት ት/ቤት አጠገብ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 26 ቀበሌ 06 አቃቂ ወንዝ ላይ በሚገኙት ባሕረጥምቀቶች ደግሞ በእያንዳንዳቸው ከአምስት አብያተ ክርስትያናት የሚወጡ ታቦታት ያድራሉ። ከጥምቀት በዓል ቀጥሎ ጥር 12 ቀን በሚከበረው የቃና ዘገሊላ በዓልም በጥምቀተ ባሕሩ ሁለት ሌሊቶችን የሚያድሩት የቅዱስ ሚካኤል አብያተ ክርስትያን ታቦታት ወደየቤተክርስትያናቸው ይመለሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ በቅዱስ ሚካኤል ስም የሚታወቁ 14 አብያተ ክርስትያን አሉ፡፡ እነዚህም በ14 የተለያዩ ጥምቀተ ባሕሮች የሚያድሩ ናቸው። በጃንሜዳ፣ በየካ ወረዳ 16 ቀበሌ 11 ኳስ ሜዳ፣ በኮተቤ ወንድይራድ ት/ቤት፣ በቦሌ ወረዳ 20 ቀበሌ 01፣ በየረር ሠፈራ አካባቢ፣ በጉለሌ ራስ ኃይሉ ሜዳ፣ በቤቴል ኳስ ሜዳ፣ በላይ ዘለቀ መንገድ አዲሱ ገበያ፣ በመንዲዳ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ፣ በመካኒሳ ወረዳ 23 ቀበሌ 04፣ በአፍሪካ አንድነት አካባቢ ወረዳ 23 ፊት ለፊት፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ጨፌ ዳዲ ሜዳ፣ በአቃቂ ወንዝና በቃሊቲ አካባቢ የሚያድሩ የሚካኤል ታቦታት በጥር 12 ነው ወደየቤተክርስትያናቸው የሚመለሱት፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ የሚካኤል ታቦትን በድርብ የያዘው የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስትያን ታቦቶችም በዚሁ እለት ነው ወደቤታቸው የሚመለሱት፡፡ በአዲስ አበባ ከጥምቀት ጋር ተያይዞ የሚከበረው የእግዚአብሔር አብ የንግሥ በዓልም በተመሳሳይ ኹኔታ ታቦታት ወደመንገዶች እና አደባባዮች በመውጣት የሚከበር ነው። በአራተኛው ቀን ጥር 13 በተመሳሳይ ሁኔታ የሚከበርባቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ የደብረ ምጽላል እግዚአብሔርአብ፣ በአዲሱ ገበያ ደብረ ሲና እግዚአብሔርአብና በጉለሌው ጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል ናቸው፡፡ ጥምቀት በአዲስ አበባ በሰሜን ከእንጦጦና ከቃሌ ተራራ ጀምሮ እስከ ደቡብ የቃሊቲ ገጠሮች ድረስ፣ በምዕራብ ከትንሹ አቃቂ ወንዝ እስከ ምሥራቅ ወንድ ይራድ ት/ቤት (ኮተቤ) ድረስ በጐዳናዎች፣ በአደባባዮችና በየማርገጃው ለአራት ቀኖች ያህል እንዲህ ባለ አጀብና ድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ ፀሐፊውን በሚከተሉት የኢ-ሜልና ፌስቡክ አድራሻ ማግኘት ይቻላል ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. / This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

Published in ህብረተሰብ

‹‹ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን ለመዘርጋት የተረቀቀው ሕግ ወደ ኋላ አይመለስም፤ መሥመሩን አይለቅም›› /ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለመዋቅርና አሠራር ለውጥ በባለሞያ ያካሔደውን የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት እንቃወማለን የሚሉ ውስን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች አይወክሉንም ሲሉ የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ልዩ ልዩ አገልጋዮችና ምእመናን ለፓትርያርክ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡ ለዘመናት የቆየው የቤተ ክርስቲያን መዋቅርና የሥራ ሒደት ከነበረው ተስፋፍቶ፣ የወቅቱን አሠራርና ሥልጣኔ የዋጀ ኾኖ በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔና በፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ በባለሞያዎች መዘጋጀቱንና ረቂቁ ወደ ታች ለግምገማ ወርዶ እንደተወያዩበት አስተዳዳሪዎቹና አገልጋዮቹ ጠቅሰዋል፡፡

የግምገማው ሪፖርት በሀ/ስብከቱ ተጠናቅሮ የሚቀርብለት ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ሳይታወቅ በሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ስም ‹‹በውስን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች›› በጥናቱ ላይ የሚቀርበው ተቃውሞና በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ የሚሰነዘረው የስም ማጥፋት ዘመቻና ውንጀላ÷ ‹‹ከመሥመር የዘለለ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ አንድነትና ጥቅም እየደከሙ ያሉትን ብፁዓን አባቶች በመድፈር ቤተ ክርስቲያኒቱን ሰድቦ ለሰዳቢ አጋልጧታል፤›› ብለዋል፡፡ ጥያቄያቸውን በአምስት ሺሕ የአስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና ልዩ ልዩ አገልጋዮች ፊርማ አስደግፈው ማቅረባቸውን የገለጹት በመቶዎች የሚቆጠሩ እኒህ አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች፣ ሀ/ስብከቱ እያካሔደው በሚገኘው የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ አቡነ እስጢፋኖስ ‹‹ወሳኝ አባት›› እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡

ከቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ውጭ በኾኑ፣ የሥነ ምግባር ጉድለትና ጠባየ ብልሹነት ባለባቸው ውስን ሰዎች ሳቢያ ምእመኑ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እንዲያመራ እየተደረገ በመኾኑ ጉዳዩ አንገብጋቢ መኾኑን በመጠቆም፣ ‹‹በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ የሚደረግ የስም ማጥፋት ዘመቻና ሰድቦ ለሰዳቢ የመስጠት ሕገ ወጥ ተግባር›› መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በዚህ ረገድ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከማስጠበቅ ጋራ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም እንዲሁም የአባቶችን ክብር ሊጠብቅና ሊያስጠብቅ የሚችል ጠበቅ ያለ ሕግ ማውጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡ የጥያቄ አቅራቢዎቹን አቤቱታ ያዳመጡት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፣ ኹሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመኾናቸው የኹሉንም ሐሳብ የመስማት ሓላፊነት ቢኖርባቸውም በተቃዋሚዎቹ በኩል የተሰማው ሕገ ወጥና ግብረ ገብነት የጎደለው ንግግር ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሰዋል፤ አኹን ደግሞ በተረጋጋ መንገድ ስለቀረበው የአስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች ጥያቄ አመስግነዋል፡፡

በባለሞያዎች የቀረበው የሀ/ስብከቱ የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ረቂቅ ወደኋላ የሚመለስበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ፓትርያርኩ ገልጸው፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና፣ ለሃይማኖት መጽናት የሚጠቅመውን ሐሳብ ኹሉ ተቀብለው እንደሚያስተናግዱ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የዘመኑ ምሁራን የተካተቱበት በቁጥር ከ9 - 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ረቂቁን ዳግመኛ እንዲያዩት መቋቋሙን ለጥያቄ አቅራቢዎቹ ያስታወቁት አቡነ ማትያስ፣ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር እንዲኖራት የተዘረጋው ሕግ ረቂቅ መሥመሩን እንደማይለቅ አረጋግጠውላቸዋል፡፡

Published in ዜና

          በህገመንግስቱ ላይ ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት፣ የህዝብን ሃሳብ በማናወጥ እና “ጨፍጫፊ” በማለት የመንግስትን መልካም ስሙን በማጥፋት የተከሰሰው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ በመከላከያ ማስረጃነት ያቀረበው የቢቢሲ ዶክመንተሪ ፊልም፣ የቢቢሲ ስለመሆኑ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ሲል ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለውሣኔ ቀጥሯል፡፡

ተከሳሹ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ቢቢሲ ያዘጋጀው ነው በሚል በመከላከያ ማስረጃነት የቀረበው የድምጽ ምስል ዶክመንተሪ ፊልም በእርግጥም የቢቢሲ ስለመሆኑ ጥያቄ በማስነሳቱ ከጣቢያው ሃላፊዎች ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ቀደም ባለው ቀጠሮ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው፡፡ ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት የተከሳሽ ጠበቃ ለፍ/ቤት እንዳስረዱት፤ ማረጋገጫውን ለማግኘት ከቢቢሲ ሃላፊዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ጠቁመው ለዚህኛው ቀጠሮ ሊደርስላቸው ባለመቻሉ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሠጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ቀደም ሲል በአቃቤ ህግ የቀረበበትን ማስረጃ ይከላከሉልኛል ያላቸውን የሰው ምስክሮች ለፍ/ቤቱ ከማሰማቱም በተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ መከራከሩ ይታወሳል፡፡

ለፍ/ቤቱ ካቀረባቸው የመከላከያ የሰነድ ማስረጃዎች መካከልም 4 ገጽ ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ (ኢሠመጉ) ሪፖርት፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “ኢትዮጵያን አመጽ አያሰጋትም” ሲሉ የሠጡት ቃለ ምልልስ፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት እንዲሁም ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ቢቢሲ በፎከስ ኦን አፍሪካ ያሠራጨውና ፍ/ቤቱ ማረጋገጫ የጠየቀበት ዘገባ ይገኙበታል፡፡ ተከሣሹ ባቀረባቸው የመከላከያ ማስረጃዎች ላይ አስተያየቱን የሰጠውን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ የቀረቡት ማስረጃዎች ከክሱ ፍሬ ሃሳብ ጋር ግንኙት የላቸውም ብሎ የተከራከረ ቢሆንም ፍ/ቤቱ ሣይቀበለው ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ በቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ላይ ያለውን አጠቃላይ አስተያየት በቀጣዩ ቀጠሮ ለማቅረብ ፍ/ቤቱን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ፍ/ቤቱም የተከሳሽን የቢቢሲ ዘገባ ማረጋገጫ ለመቀበልና የአቃቤ ህግን አጠቃላይ የማስረጃ አስተያየት ሠምቶ ውሣኔ ለመስጠት ለየካቲት 5 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

በሌላ በኩል ሐዋሣ በሚገኘው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት፤ የሃዋሣ ዩኒቨርሲቲ የ300ሺህ ብር የፍትሃ ብሔር ክስ ያቀረበባቸው የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ አሳታሚና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ደግነው እንዲሁም ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤት ቀርበው የቃል ክርክር ካደረጉ በኋላ፣ የፍ/ቤቱን ውሣኔ ለመስማት ለጥር 20 ቀን 2006 ተቀጥረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፍ/ቤቱን ሂደት ለመከታተልና ስለዘገባው ማብራሪያ ለመስጠት ወደ ሃዋሣ በሄደበት ወቅት የትራፊክ አደጋ የደረሰበት ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ስለ አደጋው ፖሊስ አዲስ አበባ ድረስ መጥቶ ቃሉን የተቀበለ ሲሆን፤ እስካሁን ግን ክስ እንዳልተመሠረተ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና
Saturday, 11 January 2014 12:28

“...እማዬ ጥሩ ሰርታለች...”

ከወሊድ በሁዋላ በቤተሰብ ወይንም በጉዋደኛ የሚደረገውን እንክብካቤ በሚመለከት ልጅ ወልደው የነበሩና እማኝነታቸውን የሚሰጡ እናቶችንና ባለሙያን ለዚህ እትም ማብራሪያ ጠይቀናል፡፡ የመጀመሪያዋ እናት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥታለች፡፡ “...እኔ ልጅ ከወለድኩ አሁን አምስተኛ አመቴን ይዣለሁ፡፡ በወለድኩኝ ሰአት እናቴ በጣም ትንከባከበኝ ነበር፡፡ ለምሳሌም ...አጥሚት ቢጠጣም ባይጠጣም ጠዋትና ማታ በፔርሙስ እየተሞላ ከራስጌዬ ይቀመጥልኝ ነበር፡፡ እናቴ አጥሚቱ መጠጣት... አለመጠጣቱን ካረጋገጠች በሁዋላም በመጠጫው ትቀዳልኝና አጠገቤ ትቀመጣለች፡፡ ጨርሼ ካልጠጣሁኝ ከአጠገቤ አት ሄድም፡፡ ...በይ ጠጪ ...ጡት ይሆናል... ትለኛለች። ገንፎ በየጠዋቱ በጭራሽ በሌላ ነገር የማይተካ ቁርስ ነው፡፡ ...ይህ እንግዲህ ገና ወፍ ሲንጫጫ እንደሚባለው ከጠዋቱ ወደ 12፡30/ ገደማ ነው፡፡ ከዚያም ረፈድ ሲል ወደ ሶስት ሰአት ገደማ ...ፍርፍር ...ቅንጬ ወይንም ደግሞ ጥብስ... ብቻ የተቻለውን ነገር አዘጋጅታ ታቀርባለች። ...እማዬ ...ገንፎው እኮ ከአንገቴ አልወረደም... ስላት ...ችግር የለም... ይህን ስትበይበት ይወርዳል... የሚል ነው መልሱዋ፡፡ ከሶስት እስከ አራት ሰአት ቁርስ ከበላሁ በሁዋላ ወደ አምስት ሰአት ደግሞ አጥሚት ይቀዳልኛል፡፡ እኔ የፈለገ ነገር ብናገር እናቴ አትሰማኝም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ ቅባቱን ቀንሺው ስላት... አጥሚቱ የተሰራው በወተት ነው... ምንም ቅባት የለበትም ትለኛለች፡፡ ...እኔ ግን ስቀምሰው... ቅቤ እንደአለበት ሳረጋግጥላት... የእሱዋ መልስ... አይ... ትንሽ ላመል ነው ያስነካሁት የሚል ነው። ...እንዲያው ባጠቃላይ የእናቴን እንክብካቤ ምንም አልረሳውም፡፡ በጣም ተጨንቃ... አልፋ ተርፋ ሌሊት ቀስቅሳ አጥሚት የምትሰጠኝ ሳይነጋ የምታበላኝ... ምንም አይረሳኝም፡፡ ፍርፍሩ.. ጨጨብሳው... ጥብሱ... ክትፎው... አረ ምኑ ቅጡ... የማይረሳኝ ነገር የአራስ ጥሪ በግ ታርዶ ሌላ ሰው እንዳይበላው ከልክላ... ብቻዬን እንድበላ የወሰነችው ውሳኔ ነው፡፡ እኔም በዚህ ጊዜ ባለቤቴን ጠርቼ... በቃ እኔ ከመሞቴ በፊት ወደቤቴ መሄድ አለብኝ ብዬ ስወስን... በትንሹ ረገብ አለች፡፡ ለማንኛውም... እናቴ ... ክብደቴን በሶስት እጥፍ አሳድጋው ከአራስ ቤት ወጥቻለሁ፡፡ ይኸው እስከዛሬ ድረስ ሰውነቴ ወደነበረበት አልመለስ ወይንም አልስተካከል ብሎ እታገላለሁ፡፡ እማዬ ጥሩ ሰርታለች፡፡ ነገር ግን ...አጥፍታለችም፡፡” ከላይ ያነበባችሁት የወ/ሮ ትእግስት አለሙን አስተያየት ነው፡፡ ዶ/ር መብራቱ ጀምበር በብራስ የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተርና የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔ ሻሊስት ማብራሪያ የሚከተለው ነው፡፡ ጥ/ ከወሊድ በሁዋላ ሊኖር የሚገባው እንክብካቤ ምን መምሰል አለበት? መ/ አንዲት ሴት በምትወልድበት ጊዜ ሊኖር ስለሚገባው ነገር ከመነጋገር በፊት ከመውለድዋ በፊት የነበረችበትን ማሰብ ይገባል፡፡ ከመውለድ በፊት የሚኖሩ የተለያዩ የጤና ሁኔታዎች በወሊድ ጊዜ ለሚኖረው ጤናማነት ወይንም የጤና መጉዋደል ምክንያት እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ አንዲት ሴት አስቀድሞውኑም የተለያዩ የውስጥ ደዌዎች ...ለምሳሌ እንደ ስኩዋር... የደም ግፊት... የልብ ሕመም... የመሳሰሉት ችግሮች ቢኖሩባት ወልዳም ይሁን ከመውለድዋ በፊት ሊደረግላት የሚገባውን በተለይም ከምግብ ጋር በተያያዘ እንክብካቤውን በምን አቅጣጫ ማድረግ እንደሚገባ ያመላክታል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ወላድዋ በምጥም ይሁን በኦፕራሲዮን ስትወልድ ሰውነትዋ ሊያገኝ የሚገባውን ንጥረ ነገር በተሟላ መልኩ ለመስጠት እንዲያስችል የተለያዩ ምግቦችን በመጠኑ ብትወስድ ይመከራል፡፡ ጥ/ ወላድዋ ወፍራም ወይንም ቀጭን ብትሆን በሚል የሚለይ አመጋገብ ይኖራል? መ/ የወለደችው ሴት ወፈረች ወይንም ቀጠነች ተብሎ የሚለይ ነገር የለም፡፡ በመሰረቱ የአመ ጋገብ ስርአት ለወላዶች ብቻ ሳይሆን... ለማንኛውም ሰው እንደጤናው እና ተፈጥሮአዊው ሁኔታው በምግብ ጥናት ባለሙያዎች በሚሰጠው ምክር በታገዘ መልኩ መመገብ ጥሩ ልምድ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ሰውነቱ የሚፈልገውን ስብ... ካርቦሀይድሬት... ኮለስትሮል... ቫይታሚን... አይረን... ወዘተ... በምን ደረጃ እንደሆነና ምን ምን አይነት ምግቦችን መመገብ እንደሚያስፈልገው የሚያማክሩ ባለሙያዎች በአገራችን በስፋት ቢገኙ ሁሉም ሰው ጤንነቱን በጠበቀ መልኩ መኖር ይችላል፡፡ ወደ ወላዶች ስንመለስ ቀደም ብሎም ይሁን በእርግዝናው ጊዜ የተከሰቱ ሕመሞች ካሉ በማገናዘብ ...ብዛትና ድግግሞሹን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሁሉም ነገሮች በመጠኑ ቢመገቡ ይመከራል፡፡ ቅባት ስኩዋር እና ጨው በምን ያህል ደረጃ ከምግብ ውስጥ መጨመር እንዳለበት አስቀድሞ መገመት ያስፈልጋል፡፡ ታሽገው የሚሸጡ ምግቦችን በሚመለከትም እንደ ቸኮሌት ወይንም ጂውስ የመሳሰሉት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሙሉ በሙሉ ስኩዋሮች ናቸውና መድፈር አያስፈልግም፡፡ ከዚህ ውጭ አልኮሆል ለወላዶች አይመከርም፡፡ የወለደችው ሴት ወፍራም ከሆነች ወይንም ቀጭን ከሆነች በሚል ልንከፋፍለው የምንችለው የአመጋገብ ስርአት ባይኖርም እንደአስፈላጊነቱ ከተለያዩ ምግቦች በመጠኑ እና በተጨማሪም አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ጥራጥሬ ዎችን የምግባቸው አካል ማድረግ ጠበቅባቸዋል፡፡” ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ልጅ ከወለደች ገና አንድ አመቷ ነው፡፡ ወልዳ በተኛችበት ጊዜ የቤተሰብዋን እንክብካቤ በጥሩ ጎኑ በፍጹም አትረሳውም፡፡ ነገር ግን ጎጂ የነበሩ ሁኔታዎችንም ከዚህ በመቀጠል ለንባብ ብላዋለች፡፡ “...አመጋገብን በተመለከተ ብዙም ችግር አልነበረብኝም፡፡ ምክንያቱም እናቴ እራስዋ ወፍራም ስለሆነች እኔ እንድወፍር ስለማትፈልግ ነው፡፡ እናቴ ለሰውነትዋ ቅርጽ መበላሸት ዋነኛዋ ተዋናይ እናትዋ እንደሆነች በመግለጽ ሁሌ ስለምታማርራት እኔም እርስዋን እንዳማርራት አትፈልግም፡፡ ስለዚህ ምግብ ይቀርባል... ብበላው ባልበላው ብዙም ግልምጫ አይደርስብኝም ነበር፡፡ በዚህ በኩል የነበረው ነገር ብዙም ችግር አልነበረ ውም፡፡ እኔ ወልጄ በተኛሁበት ጊዜ የነበረብኝ ችግር ጠያቂዎችን የማስተናገድ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ሊጠይቀኝ ሲመጣ ታሪኩን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው መስማት ይፈልጋል፡፡ የወለድሽበት ሆስፒታል የት ነው? ሐኪምሽ ማን ነበር? ሆስፒታሉ በባለሙያዎች እንዲሁም በማዋለጃ መሳሪያው ምን ያህል የተደራጀ ነው? የወለድሽው በምጥ ነው ወይንስ በኦፕራሲዮን? ለምን በምጥ አልወለድሽም ? ጡት ታጠቢያለሽ? ...ወዘተ እያንዳንዱ ጠያቂ ከላይ የዘረዘርኩዋቸውን እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ከወለድኩበት ቀን ጀምሮ ስለሚጠይቀኝ እጅግ አሰልቺው ነገር ነበር፡፡ በዚህ ላይ የመጣ ሰው ሁሉ የተወለደውን ልጅ ማየት ይፈልጋል። ማየት ሲባል ደግሞ የፊት ገጽታውን ብቻ ሳይሆን የተሸፋፈነውን አካሉን ጭምር ቢሆን የሚመርጡ በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ማንን እንደሚመስልም መልስ መስጠት ይጠበቅብኛል፡፡ ሌላው ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነገር ጠያቂ ሲባል ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ ሳሎንን አቋርጠው መኝታ ቤት በቀጥታ የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ እንደ ጉንፋን... የተለያዩ የአካል ጠረኖች... የመሳሰሉ ልጁን ሊመርዙ የሚችሉ ነገሮችን በሚመለከት ጥንቃቄ የሚያደርጉ እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ ጠያቂዎች በቀጥታ ልጄ ጋ እንዳይደርሱ ለማድረግ እኔ ወደሳሎን እየሄድኩ ማነጋገር ጀምሬም ነበር። ነገር ግን ወገቤን እያመመኝ ተቸገርኩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያንን የድሮውን የእናቶች መጋረጃ እመኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህም በመነሳት ለእራሴ ያሰብኩት ነገር ምንድነው... ማንኛዋም ሴት ስት ወልድ ...ቢያንስ እስከ አንድ ሳምንት ድረስ ለሰው መናገር አያስፈልግም ከሚል ደረጃ ደርሻለሁ፡፡ በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያቶች እናቴን በፍጹም አልረሳትም፡፡ ሳልተኛ ተኝታለች... ሳልታጠብ ሻወር ቤት ነች... ወዘተ... መልስ እየሰጠች ብዙ እረፍት እንዳ ኤልሳቤጥ ያሬድ - ከሰሚት ጥ/ ከሙያ አኩዋያ ጠያቂዎች እንዴት ይገለጻሉ? መ/ እኔ ብዙ ጊዜ የምናገረው ነገር አለ፡፡ ...ወላድዋን የምትወድዋት ከሆነ በስልክ ወይንም በፖስት ካርድ መጠየቅ ይበቃል... አትክበብዋት... የሚል ነው፡፡ ሰዎች ብዙ ጊዜ የማያስቡት ነገር አለ፡፡ የተወለደው ልጅ ወደዚህች አለም የመጣ አዲስ ፍጥረት ነው፡፡ ምንም ነገር የማያውቅ ...በሽታን መቋቋም የማይችል በመሆኑ ጥንቃቄ ልናደርግለት ይገባል፡፡ ነገር ግን ጠያቂዎች በተለይም በሆስፒታል ውስጥ ወላዶቹ ወደቤታቸው ሳይሄዱ እና ሳያመልጡዋቸው ለራሳቸው ጫናን የመቀነስ እርምጃ የሚወስዱ ይመስላሉ፡፡ ሰው ይቀነስ ...ግማሾቻችሁ ውጡ... ሲባሉ ይቆጣሉ... ከሰራተኞች ጋር ይጣላሉ... ወላድዋ እረፍት እስክታጣ ድረስ ክፍልዋን ሞልተው ...በሙቀት እና በትንፋሽ ቤቱ እስኪታፈን ድረስ አልጋዋን ከበው ይቆማሉ፡፡ ይሄ በፍጹም የዘመድ ወይንም የወገንነት ስራ አይደለም፡፡ ጭካኔ ነው፡፡ ለወለደችው ሴትም ሆነ ለተወለደው ልጅ ማሰብን ያላካተተ ነው። ስለዚህ ማንኛውም ጠያቂ ...ወላድዋም ሆነች ሕጻኑ ንጹህ አየር... በቂ እረፍት እንደሚያስፈልገው መገመት ይጠበቅበታል፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

በወጣት እና አንጋፋ ከያንያን እየቀረበ ያለው “ግጥም በጃዝ” 30ኛ ወርሐዊ ዝግጅት የፊታችን ረቡዕ እንደሚቀርብ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ በሚቀርበው ዝግጅት፤ አበባው መላኩ፣ ምንተስኖት ማሞ፣ ምስራቅ ተረፈ እና ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ግጥም፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወግ እንዲሁም መምህር እሸቱ አለማየሁ ዲስኩር የሚያቀርቡ ሲሆን የመግቢያ ዋጋው 50ብር ነው፡፡

Page 7 of 14