በግል መጽሄቶች ላይ የቀረበውን ጥናት ተቃውሟል

መንግስት የኢትዮ- ሱዳን ድንበር ጉዳይን ለህዝብ ግልፅ እንዲያደርግ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አና ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በጻፈው ደብደቤ መጠየቁን አስታውቆ፣ በጉዳዩ ላይ ከአዲስ አበባ ህዝብ ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዙን ገለጸ፡፡ ፓርቲው በሰጠው መግለጫ፣ ሰሞኑን በሚዲያዎች አጀንዳ ሆኖ የሰነበተውን የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ማሻሻል ጉዳይ በጥልቅ እየከታተለው መሆኑን አመልክቶ፣ ህዝቡ የድንበር ማካለል ሂደቱን ጉዳይ የማወቅ መብት እንዳለው መንግስት ተገንዝቦ ጉዳዩን ይፋ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡

መንግስት በሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ብቻውን የመወሰን መብት የለውም ያሉት የፖርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ በደፈናው በድንበር ጉዳይ ስምምነት ላይ ተደርሷል የሚል መግለጫ መሠጠቱ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ፓርቲያቸው ከአዲስ አበባ ህዝብ ጋር ለመወያየት ለጥር 18 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ መያዙን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የድንበር ማካለል ላይ ኤክስፐርቶች ሃሣብ እንደሚሠጡም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በቅርቡ የግል መጽሄቶችንና ኘሬሶችን በተመለከተ የቀረበውን የጥናት ውጤት አጥብቆ እንደሚቃወምና ሪፖርቱ የህብረተሰቡን ሃሣብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚገድብ በመሆኑ ሊጤን ይገባዋል ብሏል፡፡ ፓርቲው ኢህአዴግ ከዚህ ጥናት ሪፖርት በመነሣት የተወሰኑ ሚዲያዎችን ለማፈን እንደተዘጋጀ በግምገማው መረዳቱን አቶ ሀብታሙ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡

Published in ዜና

የኢትዮጵያ ታሪክ ገንኖ የሚታወቅበት ጊዜ ይመጣል
“እኔ ብቻ አውቃለሁ” የምንለው ነገር የትም አያደርስም
ዩኒቨርስቲዎቻችን በኢትዮጵያ ትምህርት አልጠነከሩም
ግዕዝ በታወቁ የዓለም ዩኒቨርስቲዎች የተከበረ ትምህርት ነው

 የአሁኑ አመጣጥዎ የተለየ ዓላማ (ተልዕኮ) አለው? ወይስ… ከ25 ዓመት በፊት “አት ሆፕ ፒስ” የሚል ድርጅት አቋቁመን ነበር፡፡ ወቅቱ የጦርነት ጊዜ ነበር። ለአገሪቱና ለህዝቡ ሰላም ለማምጣት የተመሰረተ ነበር፡፡ በኋላም ከክቡር አቶ መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማረውና) እንዲሁም ከፕሬዚዳንት ኢሣያስና ሌንጮም ጋር ተገናኝተን ተወያይተናል - በሰላም ጉዳይ፡፡ በተለይ ክቡርነታቸው የድርጅታችንን ስራ ወደውልን ነበር፡፡ ሰላሙን ለማጐልበት ይጠቅማል ብለውናል፡፡ ከዚያም አድጐ ጊዜያዊ ፒስ ኮሚቴ ሆነ - “ፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ሴንተር” በሚል ስያሜ፡፡ የድርጅቱ አባላት ኢትዮጵያን የምንወድ ሰዎች ነን። መንግስትም ህዝቡም እየተባበረ ይሠራል የሚል እምነት ስላለን፣ ከ20 ዓመት ጀምሮ አንዳንድ ሰዎች የጥላቻ ቃል ሲናገሩ “ጉዳዩን በፍቅር እንፈታለን” እያልን ከክቡርነታቸው ጋር እንማከር ነበር፡፡ “ፒስ ኤንድ ዲቨሎፕመንት” እያደገ ሄደና በ1993 ዓ.ም እዚህ ትልቅ ኮንፈረንስ ተደረገ፡፡ የሃይማኖት መሪዎች፣ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የመምህራን ማህበር እና ራሱ መንግስት የተሳተፉበት ትልቅ ስብሰባ ነበር፡፡ ከውጭ አገርም ሰዎች ጋብዘን፣ የኢትዮጵያ ፍቅርና ሠላም እንዲጠናከር ፀሎት አደረግን፡፡ ብዙ ሰው የሚያውቀው አንድ የድርጅቱ መፈክር አለ፤ “ወሬ አናብዛ፤ ስራውን እንስራ” የሚል ነው።

ብዙ ጊዜ ስራችን የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ አንፈልግም፤ አንዳንዴ እየሾለከ ቢፃፍም ብዙ ጊዜ ግን እንጠነቀቃለን፤ ፐብሊሲቲ (ራስን ማስተዋወቅ) አንወድም፡፡ እናም አመጣጤ ለዚህ ድርጅት ዓመታዊ የቦርድ ስብሰባ ነው፡፡ በዳያስፖራው ዘንድ ጭፍን የጥላቻ ፖለቲካ ይንፀባረቃል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ድርጅታችሁ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰራው ስራ አለ? ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ምክንያቱም በየጊዜው አሜሪካ ያለነው የቦርድ አባላት የምናውቃቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ለማናገርና ለማወያየት እንሞክራለን። ምንም ቢሆን አገርን ማንቋሸሽ ጥሩ አይደለም። እዚያ ተቀምጠን አገርን ማስከበር፣ ኢትዮጵያ እንድታድግ ማድረግ ነው የሚያስፈልገው፡፡ እዚያ ያሉትን ኢንቨስተሮች ሁልጊዜ እናወያያለን፡፡ የእኛ ድርጅት እንደውም በቅርቡ ስሙ ተለውጦ “ሰላምና እድገት ማዕከላዊ ማህበር” ይባላል፡፡ ሰላም ከሌለ እድገት የለም፡፡ እድገት ከሌለ ሠላም የለም። ሁለቱም የተያያዙ ናቸው፡፡ ባልና ሚስት ማለት ናቸው፡፡ እዚያ ያሉ ኢንቨስተሮች፤ ትኩረታቸውን ኢትዮጵያን በንግድና በእርሻ ለማሳደግ እንዲጥሩ እንገፋፋለን። እዚያ ቁጭ ብላችሁ መጮህ የለባችሁም እንላቸዋለን። ብዙዎቹ ሃሳባችንን ይወዱታል፡፡

ዘጠና አምስቱ ፐርሰንት ይስማማሉ። አምስቱ ፐርሰንት ደግሞ ሌላ ሃሳብ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በቅርቡ ደግሞ አንድ ፕሮጀክት ጀምረናል - “አፍሪካ ፒስ ሴንተር” የሚል፡፡ የአካዳሚክ ድርጅት ነው፤ “ኢንስቲቲዩት ኦፍ ሴሜቲክ ስተዲስ” ይባላል። ጆርናሎችና መጽሐፍት በየጊዜው እናወጣለን። በህዝብ ግንኙነትና በኮሙዩኒኬሽን ሰላም ለማምጣት የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው፡፡ ለምሳሌ “ኢንስቲቱዩት ኦፍ ሴሜቲክ ላንጉጅስ” በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ይንቀሳቀሳል። ለአረቦችና እስራኤሎች ውዝግብ አንዳንዴ ቋንቋ የመግባባት በር ይከፍታል ብለን እናምናለን፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በርም ሊዘጋ ይችላል። የእኛ ተቋም በትምህርት ላይም ተመስርቶ ህዝቡ ደግሞ እንዲቀራረብ፣ እንዲወያይ፣ እንዲግባባ፣ እንዲስማማ፣ እንዲፋቀር ይሰራል፡፡ አሁን ደግሞ መካከለኛው ምስራቅን ብቻ ሳይሆን አፍሪካንም እንጨምር ተብሎ “አፍሪካ ፒስ ሴንተር” በሚል ጀምረናል፡፡ በአፍሪካም ዓላማው ተመሳሳይ ነው? ሁለት ዓላማ አለው፡፡ አንደኛው አፍሪካ ውስጥ ያሉትንም ችግሮች ተገናኝተን እንድንወያይ፣ እንድናውቃቸው የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአካዳሚክ መንገድ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አፍሪካ አሜሪካውያን ተማሪዎች አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ከእነሱ መካከል ነው ወደ አፍሪካ ተመልሰው መሪዎች የሚሆኑት፡፡

ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ሳለሁ፤ አፍሪካ ውስጥ የነበረውን አፓርታይድ ከማንም በፊት አጥብቀው መቃወም የጀመሩት ጥቁር አሜሪካውያንና ጥቁር አፍሪካውያን ናቸው፡፡ ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲም ትልልቅ የተቃውሞ ትእይንቶች ያደርጉ ነበር፡፡ ይሄን እንቅስቃሴ በመላው ዓለም የገፉት በአሜሪካ ውስጥ ያሉት አፍሪካውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን በትብብር ነው፡፡ በአሜሪካ የሚገኙ አፍሪካውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን በአፍሪካ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር፣ ኢኮኖሚውም እንዲዳብር መተባበር ይችላሉ፡፡ በዚህ መንፈስ ነው የምንሠራው፡፡ ዲያስፖራ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ዛሬ እንደውም እንደሰማሁት፤ በዓመት ከ3 ቢሊዮን በላይ ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ይላካል - ከዲያስፖራው፡፡ ይሄ ደግሞ ለአገር ቤት በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት የምትሰሩት የመከላከል ሥራ አለ? አሁን በአገራችን ሠላም አለ፡፡ ያለው ሰላም እንዳይናድ፣ ትልቅ ዛፍ እንዲሆን እየሠራን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በመሠረቱ ተስማምቶ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ አንዳንዶቻችን አልፎ አልፎ በሀይለ ቃል ብንናገርም፤ ብንሳደብም ህዝባችን መግባባት የሚችል ህዝብ ነው፡፡ ብዙ ሀገር ዞሬ አይቻለሁ፡፡

አንድ ጊዜ ኬንያ ሄጄ፤ “ቀን ቀን አትውጣ፣ አደገኛ ነው” ተባልኩ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ስሄድ ደግሞ “ማታ ማታ አትውጣ፤ አደገኛ ነው” አሉኝ፡፡ አዲስ አበባ ግን ይሄ ሁሉ ችግር የለም፤ ሰላም ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሠረቱ ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ ባህል አለው፤ መንፈሳዊ ህዝብ ነው፤ ሰው የሚያከብር ነው፡፡ ከመካከላችን ግን አሉ፤ ሃይለኞች፡፡ በተለይ የማኪያቬሊን መጽሐፍ ያነበቡ፣ የማርክሲዝም ትምህርት ተምረው አንጐላቸው ትንሽ የዞረ ጥቂቶች አሉ፡፡ ማዕከላችሁ ከሃይማኖት መቻቻል ጋር በተያያዘ በክልሎች ጭምር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል፡፡ በዚህ ሂደት የገጠማችሁ ችግር፣ ፈተና ወይም መሰናክል ይኖራል? እኛ ብቻ አይደለንም፤ ሌሎችም ድርጅቶች አሉ፡፡ የውጭም የውስጥም “ኢንተርፌዝ” የሚባል ህብረት አለ፡፡ ዋናው ነገር ህዝቡ ውይይት እንዲያደርግ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ ትልቅ “ኢንተርፌዝ” ስብሰባ ያደረግነው እ.ኤ.አ በ1992 ዓ.ም ነበር፡፡ እኔ እራሴ አሁን ሶስት መፃህፍት እየፃፍኩ ነው - ስለክርስቲያን፣ ስለ እስላም እና ስለ ይሁዲ፡፡ እኛ አገር የተለያዩ ሃይማኖቶች ቢኖሩም ህዝቡ ከጥንት ጀምሮ ተቻችሎ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ አዲስ የምንፈጥረው ነገር የለም፡፡ ያ ባህል እንዳይጠፋ ማድረግ ነው ያለብን፡፡ የኢትዮጵያ ክርስቲያንም እስላምም ለብዙ ዘመን ተቻችሎ የኖረ ነው፡፡ እኔ በጣም የሚያስገርመኝ ወሎ ውስጥ አንዳንድ ቤተክርስቲያኖችን ገንዘብ አዋጥተው ያሠሩት እስላሞች መሆናቸው ነው፡፡

አንዴ የአርሲ ጳጳስ አቡነ ናትናኤል እንደነገሩኝ፤ ቤተክርስቲያን ሲያሰሩ ግማሹን ገንዘብ ያዋጡት ሙስሊሞቹ ናቸው፡፡ ከክርስቲያንም ከሙስሊምም ጥቂቶች ውጭ አገር ያለውን መንፈስ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ጥቂቶች ልበል እንጂ የምፈራው ጥቂቶችን ነው፡፡ ጥቂቶችም ቢሆኑ ግን “ቁስላችሁ ምንድን ነው?” ብለን ከእነሱም ጋር ቁጭ ብለን መነጋገር፣ መወያየት ያስፈልገናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ሌሎችም ድርጅቶች እየተነሱ ነው፡፡ አንዳንዶቹ “እኔ አውቃለሁ፤ የእኔ መንገድ ትክክል ነው” ይላሉ፡፡ እንደዚህ አይነት እንቅፋቶች ይኖራሉ እንጂ የከፋ ነገር እስካሁን የለም፡፡ በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን ችግር ማዕከላችሁ ለመፍታት የሚያደርገው እንቅስቃሴ አለ? በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ “አፍሪካን ሪሊጂንስ” የሚባል ትምህርት ማስተማር የጀመርኩት እኔ ነኝ፡፡ ስለእነሱ ሃይማኖት ብዙ አጥንቼአለሁ። ጥቂቶቹን የጦርነቱ ጊዜ ኬምብሪጅ መጥተው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ጥሩ ባህል ያላቸው ናቸው፡፡ ህዝቡ ትዕግስተኛና ተግባቢ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ጦርነቱና ግጭቱ የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ዘመን “ከፋፍለህ ግዛ” የፈጠረው ጣጣ ነው፡፡ የአፍሪካ ፒስ ሴንተር ሱዳንንም ለማገዝ የመስራት አላማ አለው፡፡ ብዙ ሰው የማይረዳው… ሰላምና ፍቅር እንደ ችግኝ ናቸው፡፡ ካልተንከባከቧቸው አይፀድቁም፤ ይደርቃሉ፡፡ ሰው ሲወለድ ህፃን ሆኖ ነው፡፡ ህፃን ደግሞ እስኪያድግ ጊዜ ይፈልጋል። ሰው ተወለደ ተብሎ ሜዳ ላይ አይጣልም፡፡ ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ በውጭ ያሉት ችግራቸው …የሠላም ስምምነት ተፈራረምን ብለው ቻው …ቻው ተባብለው ይለያያሉ፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ ጉዳይ የሆነውም እንዲሁ ነው፡፡ አልጀሪያ ላይ ተፈራረምን ብለው ተጨባብጠው ተለያዩ፡፡ እኛ በዚህ አናምንም፡፡ የተፈራረሙት ነገር የሠላምም ቢሆን እንዲበረታና እንዲጠነክር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጐልበት ያስፈልጋል፡፡ የታሪክ ሽሚያ ውስጥ የሚገቡት ወገኖች ናቸው ችግሩን የሚያባብሱብን፡፡ የእኛ ሰዎች መንፈሳቸው ጥሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝብ ቤተሰብ ነው፡፡ ቤተሰብ ከሆነ ደግሞ ባልና ሚስት እንኳን ይፋታል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ ህዝብ ነው፤ በባህል በቋንቋ፡፡ ግን ተፋታ፡፡ የተፋቱ ባልና ሚስትን ደግሞ ‹‹በአንድ አልጋ አብራችሁ ተኙ›› ብሎ ማስገደድ አይቻልም፡፡ ይኼ ጥሩ ህዝብ፤ ብዙ ጊዜ ግራ የሚጋባው በውጭ አካል ነው፡፡ ሁለቱን ህዝብ ትውት ስናደርጋቸው፣ ሰላምና መከባበር ይመጣል። ይሄንን የምለው በአለም ላይ ብዙ የታሪክ ሽሚያ ስለአለ ነው፡፡ የአፍሪካ ስልጣኔ ሲነሳ ግብጽ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡ በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያ የ10ሺ ዓመታት ታሪክ አላት የሚል መረጃ ተሰምቷል፡፡ ይሄ ነገር እንዴት ነው? በሁለት ደረጃ ነው የምናየው፡፡ ከሁለት መቶና ሶስት መቶ ዓመታት በፊት ፈረንጆቹ “አፍሪካ ታሪክ የላትም” ብለው ስለ ግብጽም ቢሆን ብዙ አይከታተሉም ነበር፡፡ ከናፖሊዮን ጊዜ ጀምሮ “ሮዜታ ስቶን” ተገኘና ስለግብጽ መማርና ማጥናት ጀመሩ፡፡ ስለ ግብጽ ብዙ ዕውቀት በዓለም ላይ ተበተነ፡፡ በጊዜው እንግሊዞች መጥተው ግብጽን አገኝዋት፡፡

እዛ ሳሉም ታሪኩን እያስፋፉ ሄዱ፡፡ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች አፍሪካ እንደውም ታሪክ የላትም ብለው ስለ እሷ አያጠኑም ነበር። በሌላ በኩል ታሪክ ያላቸውን እንደ ኢትዮጵያ ያሉትንም ራሳቸው ለማጥናት ነው የሚፈልጉት። ኢትዮጵያውያን ራሳችንን የምናከብር ሰዎች ነን፡፡ ቅኝ አልተገዛንም፡፡ በየዩኒቨርሲቲው በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ የግዕዝ ጽሕፈቶች አሉ፡፡ ግን ኢትዮጵያ ራሷን በአለም ላይ አላስተዋወቀችም፡፡ አሜሪካን አገር ፐብሊክ ሪሌሽንስ (ራስን ማስተዋወቅ) የሚባል ነገር አለ፡፡ በፐብሊክ ሪሌሺንስ እኛ ጐበዞች አይደለንም፡፡ ባህላችንም ስላልሆነ ይሆናል። በአንድ በኩል ቅኝ አልተገዛንም፡፡ በሌላ በኩል የራሳችን “ታሪክ አለን” ብለን ወርቅ ታሪካችንን ይዘን ቁጭ ብለናል፡፡ ኢትዮጵያ አለም ላይ እንድትተዋወቅ ከተፈለገ፣ ራስን የማስተዋወቅ ሥራ ያስፈልገናል። በመንግስትም በኩል ይሄ መጠናከር አለበት። በግልም ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ መጣር አለብን። በሃርቫርድ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ሌክቸር የሰጠሁት እኔ ነኝ፡፡ ድሮ አይሰጥም ነበር፡፡ አስታውሳለሁ፤ በጃንሆይም ጊዜ እየመጣሁ እጣጣር ነበር፡፡ ግን ድጋፍ እንኳን የሚሰጠኝ አልነበረም፡፡ እስራኤል አገር ስሄድ ዩኒቨርስቲዎች ‹‹ይሄን ሌክቸር ስጥ›› እያሉ ይሻሙኛል፡፡ ኢትዮጵያ ስመጣ ግን ማንም አይጋብዘኝም፡፡ አሜሪካም ቢሆን በየቦታው ነው የምጋበዘው፡፡ ስለ አለም ታሪክ፤ ስለ አለም ሃይማኖት፤ ስለ አለም ቋንቋ ሌክቸር እንድሰጥ ይጋብዙኛል፡፡ ከ15 ዓመት በፊት አሜሪካ ኤምባሲ ዲፕሎማቶችን ጋብዘው፣ ስለ ኢትዮጵያ ባህል፣ ስለ መጽሐፈ ሔኖክ (እኔ በፃፍኩት ዙርያ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሌክቸር ሰጥቻለሁ፡፡ በስልጣኔ ቀደምት ነን እንላለን፡፡

ነገር ግን ዓለም ይሄንን እምብዛም አያውቅልንም፡፡ ለምን ይመስልዎታል? ይሄ ፕሮፌሰሮችም የሚጠይቁት ጥያቄ ነው፡፡ በ1996 ዓ.ም ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ነበር ስለ ኢትዮጵያ ማስተማር የጀመርኩት፡፡ ከአፍሪካ ቀደም ብሎ ጥናት የተጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፡፡ ከአራት መቶ ዓመት አንስቶ ጀርመኖች ግዕዝ እያጠኑ፣ ስለ ኢትዮጵያ መመርመር ጀምረው ነበር፡፡ በመሃከል አውሮፓውያን አፍሪካን ቅኝ ሲገዙ፣ ኢትዮጵያ ቅኝ ሳትገዛ ቀረች፡፡ ያኔ ተዋት። ኢትዮጵያ ታሪኳ በተለይ ከቤተክርስቲያን ጋር የተያያዙ ሃይማኖታዊ ፅሁፎች ስላሉ የታወቀ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በ7 ቋንቋዎች ነው የተተረጐመው፣ አንዱ ግዕዝ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከመቶ ዓመት በፊት በተለያዩ የዓለም አገራት “ቼር ኦፍ ኢትዮጵያን ስተዲስ” ተቋቁመው ነበር፡፡ በኋላ አፍሪካን ቅኝ ሲገዙ፤ ስለ ሌላ አፍሪካ አገራት ማጥናት ጀመሩ። በተለይ ደግሞ ከ2ኛው የአለም ጦርነት በኋላ፣ የአፍሪካም ሁኔታ ሲለወጥ “ቼር ኦፍ ኢትዮጵያን ስተዲስ” የሚባሉት ተዘጉ፡፡ አሁን የሉም፡፡ ፓሪስም ለንደንም ይሄን ዘግተው አሁን ስለሌላ ነው የሚያጠኑት፡፡ ኢትዮጵያ ግን መሠረቱ ሃይለኛ ስለሆነ፣ ለጊዜው ያንቀላፋ ቢመስልም የሚነሳበት ጊዜ አለ። የኢትዮጵያ ታሪክ በገናናነት የሚታወቅበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ይህንን ማድረግ የምንችለው ግን ዩኒቨርስቲያችን በምዕራብ አገራት ኢትዮጵያን ሲያስተዋውቅ ነው፡፡ ያኔ በየሙዚየሞቹ የኢትዮጵያ ሙዚየሞች ይፈጠራሉ፤ በየዩኒቨርሲቲዎቹ የኢትዮጵያ ታሪክ ይጠናል፤ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያን መጪ ዘመን እንዴት ይገልፁታል? ለዚህች አገር እርስ በርስ መጋጨትና መዘላለፍ አይጠቅማትም፤ ፍቅር ነው የሚያስፈልጋት፡፡ አንዳንዴ በጣም ልቤን የሚያሳምመኝ… በኢንተርኔት የሚሰዳደቡት ነገር ነው፡፡ ይሄ መቅረት አለበት፡፡ ያለችውን ሰላም ማጠንከር አለብን፡፡

የኦነግ ግሩፕ አለ፡፡ የኦጋዴን ግሩፕ አለ… ሌሎቹም በቡድን በቡድን ተደራጅተዋል፡፡ እነዚህ ቡድኖች በሰላም ወደአገራቸው ተመልሰው ለአገራቸው እድገት መትጋት አለባቸው፡፡ ግጭትና ጠባችንን ብንተው እኮ ጉልበታችንን ለሚጠቅም ነገር እናውለው ነበር፡፡ አንድ ጠርሙስ ቤኒዚን ቢሰጠን፣ ያን ቤንዚን መኪና ውስጥ ጨምረን ብዙ ማይልስ መንዳት እንችላለን። ወይም ደግሞ እሳት ጭረን ልናቃጥለውም እንችላለን፡፡ እኛ ብዙ ጊዜ ጉልበታችንን እንደዛ ነው የምናቃጥለው፡፡ ጉልበታችንን በፍቅር፣ በሠላም፣ በስራ ላይ አናውለውም፡፡ እሱን ማድረግ አለብን። መወያየት፤ መደማመጥ አለብን፡፡ እኔ አውቃለሁ የምንለው ነገር የትም አያደርስም፡፡ ሶቅራጠስ “ብዙ ባወቅሁ ቁጥር አለማወቄን ነው ያወቅሁት” ብሏል፡፡ እኔ ራሴ ወጣት እያለሁ ብዙ ነገር አውቃለሁ እል ነበር፡፡ ሰው እያደገ፣ እያወቀ ሲሄድ ግን ገና ብዙ እንደሚቀረው እየተረዳ ይመጣል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የትምህርት ሁኔታ ምን ይላሉ? የእኛ ዩኒቨርስቲዎች በኢትዮጵያ ትምህርት አልጠነከሩም፡፡ የኢትዮጵያ ትምህርት መስፋፋት አለበት፡፡ በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምዕራብ፣ በምስራቅ ያለው ህዝብ ሁሉ ታሪክ አለው፡፡ በግሪክ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ራስን ማወቅ ነው ይባላል፡፡ የ10ሺ ዓመት ታሪክ የምንለው በአለም ጐልቶ እንዲታይ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የግዕዝ ዲፓርትመንት ያስፈልገዋል …ራሱን የቻለ ከፍ ያለ ትልቅ ሙዚየም ብናዘጋጅ፣ ይህንን አይተው የውጭ ጐብኝዎች ይሳባሉ፡፡ በተለያዩ የዓለም አገራት ዞረዋል፡፡ በእንግሊዝ ሙዚየም በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በሌሎች አገራትስ? ከአውስትራሊያ በቀር ሌላውን ዓለም ሁሉ አዳርሻለሁ፡፡ በእንግሊዝ አገር ሙዚየም ውስጥ አንድ ሺ ያህል የግዕዝ መፃህፍት አሉ፤ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የተወሰዱ፡፡ በፓሪስም ወደ 2ሺ የሚሆኑ የግዕዝ መፃህፍቶች አሉ፡፡ በቫቲካን (ሮም) ውስጥ ወደ 2ሺ የሚሆኑ አሉ፡፡ እኔ ራሴ ሁለት ካታሎግ ጽፌያለሁ፡፡ አሜሪካ ውስጥ በየዩኒቨርሲቲው 500 የሚሆኑ የግዕዝ መፃሕፍት አግኝቻለሁ፡፡ ወደ 15 በሚሆኑ ዩኒቨርስቲዎች ማለት ነው፡፡ ዩኒቨርስቲዎቹ የግዕዝ መፃሕፍትን ለምንድነው የሚፈልጓቸው? እንደ ጌጥ ነው የሚቆጥሩት፡፡ ማንስክሪፕት አለን ብለው ያስቀምጡታል፡፡ ዋጋው ደግሞ ከፍተኛ ነው። በደርግ ጊዜ ብዙ መፃሕፍት ወደ ውጭ ወጥተዋል፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ሰውዬ የግዕዝ መጽሐፍት ይዞ መጣ እና አየሁት፤ በጣም ድንቅ ነው፡፡ “ምን ልታደርገው ነው?” ብዬ ስጠይቀው “ሙዚየም አለኝ፤ እሸጠዋለሁ” አለኝ፡፡ “በስንት ብር ነው የምትሸጠው?” አልኩት፡፡ “250ሺ ዶላር” አለ፡፡ አያሳዝንም፡፡ ከኢትዮጵያ አውጥተው እኮ ነው፡፡ አንድ ሰውዬ ደግሞ ከዚህ መጽሐፈ ሄኖክን አምጥቶ ሸጧል አሉ፡፡ ኢትዮጵያ እነዚህ ቅርሶችዋ እንዲመለሱላት መጣጣር አለብን፡፡ ባይመለሱ ደግሞ ጥናቱ እንዲስፋፋ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ እንቅስቃሴውን እንደዚህ ነው መጀመር ያለብን፡፡

በአሜሪካ ግዕዝን የሚያስተምሩ ዩኒቨርስቲዎች የትኞቹ ናቸው? እኔ ራሴ ግዕዝን ሃርቫርድ፣ ፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ፔኒስላቫንያ አስተምሬያለሁ፡፡ ግዕዝ እኮ የታወቀና የተከበረ ትምህርት ነው፡፡ እስራኤልም በየዩኒቨርስቲው በደንብ ያስተምራሉ፡፡ ግዕዝ፤ ከታላላቆቹ የግሪክና የላቲን ቋንቋዎች እኩል ነው የሚታየው፡፡ እኛ እኮ ነን ዋጋውን የማናውቀው፤ ሌሎቹማ ያውቃሉ፡፡ የኢትዮጵያን የጥንት ሥልጣኔና አሁን ያለችበትን ሁኔታ እንዴት ይገልፁታል? ከ1ሺ 5 መቶ ዓመት በፊት ከሮቆፒያንስ የሚባል የግሪክ ፀሐፊ፤ ከዓለም ሶስት ታላላቅ መንግስታት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ጠቅሶ ነበር፡፡ ሁለቱ ሮማና ፐርሺያ ናቸው፡፡ ያን ጊዜ ኢትዮጵያ በዚያ ደረጃ ላይ ነበረች፤ ከአለም ታላላቅ መንግሥታት አንዷ፡፡ አሁንም በጥቁር ህዝብ ዘንድ ትልቅ ተስፋ አለ፤ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ሆና እንደምትነሳ፡፡ ያንን ለማድረግ ህዝባችን በፍቅርና በሰላም መንግስቱን እያከበረ፣ መንግስትም ህዝቡን እያከበረ አብሮ የመስራት መንፈስ መፈጠር አለበት፡፡ ለእኔ ኢትዮጵያ ቁጭ ብላለች እንጂ ወደኋላ አልተመለሰችም (ሳቅ) አሁን ደግሞ የማደግ፤ የመመንደግ ዕምቅ አቅም አላት፡፡ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቦታዎች ለመጐብኘት በቂ ጊዜ አግኝተዋል? አዎ፡፡ ሁሉንም ጐብኝቻለሁ፡፡ ግዕዝ ለ2 ዓመት ተምሬያለሁ፡፡ ቅኔም ትንሽ ጊዜ ተምሬያለሁ፡፡ ያልሄድኩበት አገር የለም፡፡ በተለይ በሰሜን በኩል ደብረ ሊባኖስ፣ ላሊበላ፣ አክሱም፣ ወዘተ…ብዙ ገደማትን ዞሬአለሁ፡፡ ዶክትሬቴን የሰራሁት ስለ መጽሐፈ ብርሃን ነው፤ በአፄ ዘርያቆብ ዘመን የተፃፈ ነው፤ በውጭ አገር ታትሟል፡፡

ፈጣሪ በየትውልዱ የራሱን ድምጽ ያወጣል
ፍቅር ያሸንፋል-- የኔ ሳይሆን የትውልድ ድምጽ ነው
እዳ አለ የምንል ከሆነም፤ እዳ የሚከፈለውና የሚሸፈነው በፍቅር ብቻ ነው

“ከታሪክ ከወረስነው ቂም ይልቅ የምናወርሰው ፍቅር ይበልጣል”

የፍቅር ጉዞ ከሚለው ሃሳብ እንጀምር፡፡

መነሻው ምንድነው? “አቦጊዳ ብዬ፣ ፊደል “ሀ”ን ቆጥሬ፤

የፍቅርን ትርጉም ለልቤ አስተምሬ፣

ይዤሽ በአኮፋዳ እንደቆሎ ተማሪ፣

አቦጊዳ ልበል የፍቅር ጀማሪ…”

እንዲህ ነው የኔ የዘፈን ህይወት የሚጀምረው። አሁን የፍቅር ጉዞ ላይ ደርሷል፡፡ ሁላችንም፣ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ውስጥ እናልፋለን። ብዙ ቅሬታና ብዙ ደስታ፣ ብዙ ትክክል የሆኑ ነገሮችና ብዙ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች አሉበት - ያለፍንበት ታሪክ፡፡ ትልቁ ነጥብ፣ ካለፍንበት ታሪክ ተነስተን ለሚቀጥለው ጊዜ ምን እናድርግ የሚለው ነው፡፡ ያዘንበትን ነገር በይቅርታ ሰርዘን፣ የወደድነውን ነገር ደግሞ አሳድገን ለመጓዝ፣ ትልቁ መድሃኒት ፍቅር ነው፡፡ ይቅር ተባብሎ የቀድሞ ስህተቶችን ለማስተካከልና በህብረት ተጠራርቶ የቀድሞ ትክክለኛ ነገሮችን ለማሳደግ፣ ፍቅር ያስፈልጋል፡፡ አቡጊዳ ብለን ነው ፍቅርን የምንጀምረው፡፡ “ዳህላክ” ላይም፣ ለልጆቻችን ቂምን አናውርስ ብለናል፡፡ “ካስተማርሽው ፍቅርን በጊዜ፣ አይሻለሁ ወይ ባሱ ጊዜ…” ኢትዮጵያና ኤርትራ ተራርቀው የተፈጠረው ግጭት የሩቅ ጊዜ ታሪክ አይደለም። የብዙዎችን ህይወት በቀጠፈው ግጭት፣ ብዙ የተበተነ ቤተሰብ፣ የደማ ስሜት አለ፡፡ ይሄ ቁስል ዘላለም እንደመረቀዘ መቀጠል አለበት? መዳን መፈወስ የለብንም? ይቅር መባባልን ነው በ“ያስተሰርያል” የዘፈንነው፡፡ ለምንወልዳቸው ልጆች፤ ለምንፈጥራቸው አዲስ ትውልዶች የምናወርሰው ቂምን ከሆነ፣ ያለፈው መቁሰል ሳይበቃ ለወደፊትም ሌላ አደጋ እንዲፈጠር እየተባበርን ነው ማለት ነው፡፡ የሚሻለው መፍትሔ፣ እኛ የወረስነው አለመግባባት ካለ፣ በቂም ሰበብ የተቋሰልነው ነገር ካለ፣ የአዲሱን ትውልድ ህይወት እንዳያውክ፣ እኛ ጋ መቆም አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

የዘመናችን ፈተናዎች ሳያንሱ፣ የቅርብ ጊዜ የቂም ታሪክንም እየተሸከመን፣ ከዚያም አልፎ የሩቅ ጊዜ የቅሬታ ታሪኩንም እየቆሰቆስን ቂምን የምናወርስ ከሆነ፣ ለማናችንም ሕይወት የማይጠቅም፣ የልጆቻችንንም ተስፋ የሚያጨልም አደጋ እየፈጠርን እናልፋለን፡፡ ቂምን መሻር፣ ቁስልን መፈወስ፤ ከዚያም አልፎ ለሁላችንም የሚበጅና የተስፋ ብርሃንን የሚያደምቅ ነገር መስራት የምንችለው በፍቅር ነው፡፡ ከ “አቡጊዳ” እስከ “ያስተሰርያል”፣ “ዳህላክ”፣ ቀላል ይሆናል”…እና ሌሎች ዘፈኖች ይህንን መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ግን ልዩ አዋቂ ስለሆንኩ ወይም ልዩ ሃይል ስላለኝ አይደለም፡፡ በፈጣሪ ሃይል ነው። ፈጣሪ በየትውልዱ የራሱን ድምጽ ያወጣል። የትውልዱን ድምጽ በኔ አድርጐ ማውጣቱን አምናለሁ፡፡ አሁን፣ ቅን እና ጥሩ ትውልድ አለ፡፡ የዚህ ቅን ትውልድ ድምጽ የፍቅር ድምጽ ነው። ግራ የሚያጋቡ፣ የሚያስጨንቁና የተተበተቡ ችግሮች ሁሉ በፍቅር ይፈታሉ፡፡ ከቂም፣ ከቁስል በፍቅር እንዳን፣ ፍቅር ያሸንፋል የሚለው መልዕክት የኔ ሳይሆን የትውልድ ድምጽ ነው፡፡ ይህ ቅን ትውልድ ተቀራርቦ፣ ተሰባስቦ አንድ ላይ የፍቅር ድምፁን የሚያስተጋባበት እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው የፍቅር ጉዞ፡፡

በፖለቲካም ሆነ በሌላ ምክንያት፣ በተለያየ ችግርና አለመግባባት በአገራችን ለተከሰተው ቂምና ቁርሾም፣ እዚህ አገር ቤትም ሆነ በየአገሩ ተበታትነው የሚገኙ ወገኖቻችን፣ ቢያንስ ለልጆቻቸው ሲሉ ይቅር መባባልን እንዲቀበሉ ለመጋበዝ፤ የአዲሱ ትውልድ ስሜትም ይሄ እንደሆነ የሚገልፁ ዝግጅቶችን ለማቅረብ ነበር ያቀድነው፡፡ ዝግጅቱን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በስፋት ለማዳረስ ነው፤ በሄኒከን ከሚተዳደረው በደሌ ቢራ ጋር ተነጋግረን ውል የተፈራረምነው፡፡ በተፈራረምንበት እለት እንደተገለፀውም፤ የቋንቋና የብሔር ስብጥር ውስጥ ህብረትና አንድነታችንን የሚያጠናክር፣ ቂም እንዳንወርስና መልካም መንፈስን ለመጋራት አንድ ላይ የሚጮህ የፍቅር አላማ ያለው ዝግጅት ነው፡፡ ግን፣ የኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ የኢትዮጵያውያን ሕይወት አንተ እንደምትለው፣ በፍቅርና ሰላም ብቻ የተሞላ ሳይሆን፣ በቂምና በግጭትም የተበረዘ ነው፡፡

አይደለም? ምን ጥርጥር አለው! ያሉና የነበሩ ነገሮች ናቸው፡፡ የህይወት እና የደስታ ውድነት ትርጉም የሚኖረው ከሞትና ከሀዘን ጋር ነው፡፡ የፍቅር ውበት የሚጐላው፣ ከጥላቻ ጋር ሲነፃፀር ነው። ነገር ግን ያሳዘኑን ነገሮች ላይ ብቻ ስናተኩር፣ አዲሱንና የወደፊቱን ትውልድ ያውካል፡፡ እዳ አለ የምንል ከሆነም፤ እዳ የሚከፈለውና የሚሸፈነው በፍቅር ብቻ ነው፡፡ ፍቅር መድሃኒት ነው፡፡ የነገር ሁሉ መጀመሪያና መጨረሻ ነው፡፡ ሁላችንም ህፃናትን ማቀፍና መሳም የምንወደው ለምንድነው? ገና ሲወለዱ፣ ገና ከመነሻው ሲፈጠሩ ፍፁም ፍቅር ስለሆኑ ነው፡፡ ያ የፍቅር ሃይል ነው የሚስበን፡፡ ህፃኑም እናቱ ጉያ ውስጥ የሚገባው በፍቅር ሃይል ነው፡፡ እንኳን ሰውን የመሰለ ክቡር ፍጥረት ይቅርና አውሬ የምንላቸው እንስሳት ውስጥም የምናየው የተፈጥሮ ሃይል ነው፤ ፍቅር፡፡ ነገር ግን በኑሮ ውስጥ በብዙ ውጣ ውረድ፣ ብዙ ቅሬታዎችና እንከኖች ስለሚያጋጥሙን ፍቅራችንን ሊበርዙብን ወይም ውስጣችንን መርዘው የውስጥ ህመም ሊሆኑብን ይችላሉ፡፡ ባዘንበትና በተቀየምንበት ነገር ላይ ቆመን ተውጠን ስንቀር በሽታ ይሆኑብናል፡፡ ለቅያሜ እልባት እየሰጠንና እየሰረዝን ካልሄድን፣ ይባስ ብለን ለልጅ ልጅ እያወረስን ከቀጠልን፣ በማህበረሰብ ደረጃ እንደዝገት ውስጣችንን እየበላ ይጨርሰናል ወይም እንደተዳፈነ እሳት በሆነ አቅጣጫ ተግለብልቦ ያቃጥለናል፡፡

እና ምን ይሻለናል ብለን ስናስብ፣ በቀድሞ ዘመን ወይም ባለፍንበት ጊዜ የተፈፀሙ መልካም ነገሮችን ወይም ስህተቶችን እንዳልነበሩ ማድረግ አንችልም። ወደኋላ ተመልሰን በህይወት የሌሉ ሰዎችን መሸለም ወይም እዳ ማስከፈል አንችልም፡፡ እነሱ በዘመናቸው አልፈዋል፡፡ ነገሩ ያለው የዛሬ ነዋሪዎች ላይ ነው፡፡ በቀድሞ ሰዎች ታሪክ የምንደሰትበትና የምናዝንበት፣ ትክክል የሆኑና የተሳሳቱ ስራዎች፣ የወደድነውና የተቀየምንበት ነገር ይኖራል፡፡ ቀጥለው የመጡ ትውልዶች የትኛውን ስሜት መያዝ፣ የትኛውን ስሜት ማውረስ አለባቸው? እኛስ የትኛውን ወርሰን የትኛውን ማሳደግ አለብን? ቅሬታና ቂምን ይዘው ያወርሱናል ወይስ ፍቅርንና መዋደድን? ቅያሜና ቂም ብንወርስ ምን ይበጀናል? ወደ ኋላ ተመልሰን እዳ ማስከፈል አንችል? ህይወት የሚቀጥለው፣ ካለው ነገር ላይ በመነሳት ነው፡፡ ስህተቶችን ትተን፣ ትክክል የሆኑትን ይዘን፣ ያን እያሳደግን ነው መቀጠል ያለብን፡፡ ታላላቆቻችን በተለያዩ አለመግባባቶች ውስጥ ያልፋሉ፡፡ አለመግባባትና ቅሬታ ባይፈጠር መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ቢያንስ፣ የታላላቆችን አለመግባባት ወደ አዲሱ ትውልድ እንዳይሻገርና መጪውን ጉዞ እንዳያውክብን፣ ታላላቆቻችን ስለ አዲሱ ትውልድና ስለመጪው ትውልድ መጨነቅ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አስባለሁ። ፍቅር ያሸንፋል የሚለው የታናናሾች የአዲሱ ትውልድ ድምጽም ጐልቶ መሰማት እንዳለበት አምናለሁ፡፡ የፍቅር ጉዞ የዚህ የአዲሱ ትውልድ መንፈስ ነው፡፡ የፍቅር ጉዞ ዝግጅት ከበደሌ ቢራ ጋር ተፈራርመህ በሳምንቱ ነው ውዝግብ የተፈጠረው። እንዴት ነበር የሰማኸው? ከጊዜ በኋላ ነው የሰማሁት፡፡

አንደኛ በድሬዳዋ አንድ ተብሎ የሚጀመረው ጉዞ፣ ትልቅ የፍቅር መልዕክት የያዘ ስለሆነ፣ ያልተበታተነ ትኩረት ይፈለጋል፡፡ ከዚህ ውጭ ባለው ጊዜ ደግሞ፣ በሚቀጥለው መስከረም ወይም ብዙ ሳይቆይ አዲስ አልበም ለማድረስ የጀመርኩት ስራ አለ፡፡ ሁለቱም ቀናተኛ ስራዎች ናቸው፡፡ አእምሮህ ሌላ ነገር እንዲያስተናግድ አይፈቅዱልህም፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ባልደረቦቼ በኢንተርኔት በተፈጠረው ውዝግብ ዙሪያ ሊያናግሩኝ ሲሞክሩ ስራ ላይ ሆኜ ብዙም ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡ ሲደጋገም ግን ሰማሁ፡፡ ማኔጀሬ (ዘካሪያስ) ተጨንቆ ነው የነገረኝ። ከሥራ አስኪያጅ አንፃር ሆነህ ስታየው መጨነቁ አይገርምም፡፡ ግን ተረጋግተን ነው የተነጋገርነው፡፡ አልተረበሻችሁም? ነገሩን አቅልለን አላየነውም፡፡ የፍቅር ጉዞ ትልቅ ዝግጅት ነው፡፡ ነገር ግን፣ በብዙ ወጣ ገባ መንገድ ከማለፍ እና ብዙ ውጣ ውረድ ከማየት የተነሳ፣ ችግሮችን ማስተናገድ ትለማመዳለህ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የፍቅር መልእክት፣ በቴዎድሮስ ካሳሁን የተፈጠረ ሃሳብ አይደለም፡፡ የነበረ ያለና የሚኖር የእግዚአብሔር ሃሳብ ነው፡፡ ያንተ ድርሻ ያ ሃሳብ ሲሰጥህ መቀበል ነው እንጂ፤ አንተ ከምትጨነቀው በላይ ከምንም አስበልጦ፣ ፈጣሪ ስለ አላማውና ስለሃሳቡ፣ ስለ እኛ እና ስለትውልዱ ስለሚጨነቅ፣ ብዙ አልተሸበርንም፡፡ ሁሉንም ነገር ለበጐ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

“ጥቁር ሰው” በሚለው ዘፈንህ በአድዋ ጦርነት ዙሪያ ምኒልክንና ሌሎች የታሪክ ሰዎችን በማንሳት ዘፍነሃል፡፡ የምኒልክ ታሪክ ላይ ያለህን አስተሳሰብ በቅርቡ ቃለ ምልልስ አድርገህ በመጽሔት ታትሟል፡፡ ከዚህ ቃለ ምልልስ ጋር ተያይዞ ነው የምኒልክ ጦርነት ቅዱስ ነው የሚል አወዛጋቢው አባባል የተሰራጨው፡፡ በመጽሔት ታትሞ በወጣው ቃለምልልስ ላይ፣ እንደዚያ አይነት አባባል የለም፡፡ “አካሄዱን ያየ አመጣጡን ያውቃል” በሚል ርዕስ በእንቁ መጽሔት ታትሞ የወጣውን ቃለምልልስ ማየት ይቻላል፡፡ በምኒልክ መቶኛ የሙት ዓመት መነሻነት የተደረገ ቃለምልልስ ነው፡፡ በዚህ ቃለምልልስ ውስጥ ማንንም የሚያስቀይም አባባል የለበትም፡፡ ነገር ግን በኢንተርኔት ሲሰራጭ የኔ ያልሆነ አባባል ታክሎበት የተከፉ ሰዎች እንዳሉ ስሰማ፣ የተሳሳተውን መረጃ ለማስተካከል ምላሽ ሰጥተናል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን፣ የመጽሔቱ አዘጋጅም አወዛጋቢው አባባል እኔ የተናገርኩት እንዳልሆነ፣ በመጽሔቱ ህትመት ውስጥም እንዳልነበረ አስረድቷል፡፡ ነገር ግን ውዝግቡ በዚህ አልተቋጨም፡፡ ለምን የፍቅር ጉዞን የሚያስተጓጉል ነገር ተፈጠረ አልልም፡፡ እዚህ ምድር ከተገለጡትም ሆነ ካልተገለጡት ሃይሎች ሁሉ የሚልቀው ፍቅር ነው፡፡ ክብደቱም የዚያኑ ያህል ነው፡፡

ስለዚህ የፍቅር ጉዞ ብለህ ስትነሳ፣ ያለ እክል እና ያለ ችግር ትደርሳለህ ማለት አይደለም፡፡ እንኳን ትልቁና ከባዱ ጉዞ ላይ ይቅርና፣ እንደ ቀላል የምናያቸው ጉዞዎች ላይም፣ ወደ ናዝሬት ወይም ወደ አዋሳ ለመሄድ ስትነሳ እንኳ፣ በመኪኖች መጨናነቅ ጉዞህ ሊጓተት ይችላል። ጐማ ቢተነፍስ ወይም ሞተር ቢግል፣ ጐማ ለመቀየርና የራዲያተር ውሃ ለመለወጥ መቆምህ አይቀርም፡፡ ከሁሉም የከበደው የፍቅር ጉዞ ላይማ፣ ለምን ፈተና ይፈጠራል ማለት አይቻልም። ከምንም በላይ ይቅር መባባልን የሚያበዛ የእርቅ መንፈስን ይዘህ ስትጓዝ፣ እንዲያውም ከተቻለ ታላላቆችህም እንዲግባቡልህና መግባባትን እንዲያወርሱ ስትጮህ፣ በዚህ ምክንያት ካንተ ጋር የማይግባባ ነገር ሲፈጠር፣ ነገሩን ንቀህ የምታልፈው አይሆንም፡፡ ምንም እንኳ፣ በተሳሳተ መረጃ ምክንያት የተፈጠረ ቅሬታ ቢሆንም፣ አንተም በተራህ የቅሬታ ባለቤት መሆን የለብህም፡፡ ፍቅር ሁሉንም ያቅፋል፡፡ በተሳሳተ መረጃ የተነሳ ያልወደደህንም ሰው ማቀፍ አለበት። የቃለምልልሱ ሁለተኛ ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት ይጠብቁን፡፡

Sunday, 19 January 2014 00:00

ጐንደርን በጨረፍታ

ሱዳናውያን የአዝማሪ ቤቶች ደንበኛ ናቸው ጐንደር የዘመናዊ ከተማ ገጽታ አልተላበሰችም

ጐንደርና ቅርስ

በኢትዮጵያ የቅርስ ሀብታሞች ከሆኑ ከተሞች በቀዳሚነት ትጠቀሳለች - ጐንደር፡፡ ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የነገስታት ቤተመንግሥቶች በአለም ቅርስነት ተመዝግበው ሁነኛ የቱሪዝም መስህብ በመሆን ከፍተኛ ገቢ ለከተማዋ እያስገኙ ነው፡፡ የዳሽን ተራራ፣ የፋሲለደስ ግንብ፣ የደብረብርሃን ስላሴ ቤ/ክርስቲያን መጐብኘት ካለባቸው ታሪካዊ ስፍራዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በቅርስ አጠባበቅ ረገድ ግን ብዙ ቸልተኝነት ይታያል፡፡ ጥንታዊ ቅርሶችን እየጠበቁ፣ ጐን ለጐን ከተማዋን በማዘመን ረገድም ገና ብዙ ይቀራል፡፡ ዘመኑ የውድድር ነውና ከከተማው አስተዳደር ብዙ ትጋት ይጠበቃል፡፡

ሱዳንና አዝማሪ ቤቶች ጐንደር በርካታ የአዝማሪ ቤቶች አሏት፡፡ ህዝቡም እስክስታና ጭፈራ ነፍሱ ነው፡፡ ታሪካዊ መስህቦችን ሲጐበኝ የዋለው ቱሪስትም ምሽቱንና ሌሊቱን በአብዛኛው የሚያሳልፈው በእነዚህ አዝማሪ ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ እነሱም እኮ የጉብኝቱ አካል ናቸው፡፡ ጐንደር ደርሶ አዝማሪ ቤቶችን ያላየ የጐንደርን ሙሉ ምስል ሊያገኝ አይችልም፡፡ የደስቃና የዋንጫ ልቅለቃ ጭፈራዎች በሚደምቅላቸው በእነዚህ አዝማሪ ቤቶች፤ ሱዳኖችም ቤተኞች ናቸው፡፡ በጐንደር ባህላዊ ዘፈኖች ትከሻቸውን የሚነቀንቁ ሱዳናውያን በብዛት ሲዝናኑና ሲሸልሙ ነው የሚያድሩት፡፡ አዝማሪ ቤቶች ጥሩ የመዝናኛ ስፍራ የሆናቸው ይመስላሉ፡፡ ለጥምቀት ጐንደር ከአካባቢው ነዋሪዎች እንዳገኘነው መረጃ፤ በጥምቀት በዓል ጐንደር ትደምቃለች፡፡ እንግዶቿ ስለሚበዙም ማረፍያ ክፍሎች ማግኘት አይቻልም፡፡

ከተገኙም ዋጋቸው አይቀመስም፡፡ በጥምቀት የጐንደር እንግዶች የውጭ ቱሪስቶች ብቻ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን የበዓሉ ታዳሚዎች ጭምር ናቸው - ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ወደ ጐንደር የሚፈሱ፡፡ ለዚህ ታላቅ በዓል መስተዳድሩ የእግረኛ መንገዶችን በማንጠፍና በማስተካከል ተጠምዶ አስተውለናል፡፡ ዝግጅቱ መልካም ቢሆንም “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” አስመልስሎበታል፡፡ ኑሮና ጐንደር አንዴ አሉ፤ ኑሮ ተወደደ፤ በጐንደር፡፡ እናም ኩንታል ጤፍ 1500 ብር ገባ፡፡ አንዲት እናት ምን አሉ መሰላችሁ? “ለመሆኑ በዶላር ስንት ነው?” ነገሩ እውነት ይሁን አይሁን ማረጋገጥ ባልችልም ብዙዎች እንደሚሉትና እኔም እንደታዘብኩት ኑሮ በጐንደር በጣም ውድ ነው፡፡ የቱሪስቶች አገር ስለሆነች ነው መሰለኝ ሁሉ ነገር ዋጋው አይቀመስም፡፡ በዚያ ላይ ተከራክሮ ማስቀነስ የሚባል ነገር የለም፡፡ አንዴ የተጠራ ዋጋ አይለወጥም፡፡

ያለው ይገዛል፤ የሌለው ይሄዳል፡፡ በተለይ የባህላዊ እቃዎች ዋጋ ከመጠን በላይ ውድ ነው፡፡ ጐጆ ሰፈርና ጐንደር ከቅዳሜ ገበያ ራቅ ብሎ የሚገኘው አካባቢ ጐጆ ሰፈር ይባላል፡፡ በዚህ ሰፈር 83 በጐጆ ቅርጽ የተሰሩ የላስቲክ ቤቶች ሲኖሩ ከ250 በላይ ቤተሰቦች ይኖራሉ፡፡ እኒህ ነዋሪዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ሥራ ፍለጋ ወደ ጐንደር ተሰደው የመጡ ናቸው - ከ17 ዓመት በፊት፡፡ ዛሬም ግን የከተማው መስተዳድር አያውቀንም ይላሉ - ነዋሪዎቹ፡፡ መብራትና ውሃ፤ የመፀዳጃ ቤቶች እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ አብዛኞቹ በልመና የሚተዳደሩ ሲሆን አቅም ያላቸው የቀን ስራ እየሰሩ ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ፡፡ ከሰፈሩ ነዋሪዎች ውስጥ 21 ያህሉ የኤችአይቪ ህሙማን መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡ የጐጆ ሰፈር ነዋሪዎች ህፃናት ይበዙበታል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ህፃናትን ይዘው በመለመን የመጽዋቹን ልብ ለማራራት እንደሆነ ራሳቸው ይናገራሉ፡፡ ጐንደርና ልማት ጐንደር ነቃ ነቃ ማለት የጀመረችው በቅርቡ እንደሆነ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በየቦታው አዳዲስ ህንፃዎችና ግንባታዎች ይስተዋላሉ፡፡ አሁንም ግን ገና የዘመናዊ ከተማ መልክና ቅርጽ አልተላበሰችም፡፡ አንዳንዶች ግን ዘመናዊ የማትመስለው በተፈጥሯዊ መልክአ ምድሯ የተነሳ ነው ይላሉ፡፡ ተራራና ወጣ ገባ የበዛባት ከተማ በመሆኗ እንደማለት፡፡

ጥረት ይፈልግ ይሆናል እንጂ እቺን የጥንታዊ ሥልጣኔ እምብርት የሆነች ከተማ፣ ዘመናዊ መልክና ገጽታ ማላበስ አስቸጋሪ አይመስለኝም፡፡ ብዙ ልፋትና ኢንቨስትመንት ግን ይጠይቃል፡፡ የጐንደር ጌጥ በ1940ዎቹ የተመሠረተው ጐንደር ዩኒቨርሲቲ፤ ለከተማዋ ሁሉነገሯ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ውበቷና ጌጧ፡፡ ዩኒቨርስቲው የከተማዋ ጌጥ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ለነዋሪዎች የሥራ እድል እንደፈጠረ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርስቲው ህብረተሰቡን በተለያዩ መንገዶች ያገለግላል፡፡ የጤና ተማሪዎች በየጤና ጣቢያውና በየሆስፒታሉ ነፃ የህክምና አገልገሎት ሲሰጡ፤ የህግ ተማሪዎች ደግሞ አቅም ለሌላቸው ነፃ የህግ አገልግሎት በመስጠት እገዛ ያደርጋሉ፡፡ የቱሪዝም ተማሪዎች በበኩላቸው፤ የአካባቢው ባህል እንዳይጠፋና እንዳይበረዝ ቱባ ቱባ ባህሎችን በማስተዋወቅ፣ የመጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ ዩንቨርሲቲው በዚህ ብቻ ሳይወሰን በከተማዋ ውስጥ ለሚካሄዱ ልማቶች በገንዘብም ሆነ በእውቀት የቻለውን ያህል እንደሚያደርግ ከዩኒቨርስቲው ሃላፊዎች የተነገረን ሲሆን በሰኔ ወር የሚመረቅ ትልቅ ሆስፒታልም እያስገነባ ነው፡፡ በእርግጥ ይሄ ሆስፒታል ዘግይቶ ነው እንጂ ግንባታው አምና መጠናቀቅ እንደነበረበት ለማወቅ ችለናል፡፡

Published in ህብረተሰብ

ባለፈው ሳምንት የ1953ቱን ግርግር ምክንያት አጥንቶ የሚያቀርብ አንድ ኮሚቴ ንጉሱ ማዋቀራቸውንና ኮሚቴውም ለዚያ ሁሉ ሰው እልቂት ሰበብ የሆነውን ጉዳይ ሲመረምር ሌላ ሳይሆን ራሳቸው ንጉሰ ነገስቱ መሆናቸውን ማረጋገጡ፤ ሆኖም “የዚህ ሁሉ ወንጀልና እሱን ተከትሎ ለተፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት ኃላፊውና ሰበቡ እርስዎ ነዎት” ብሎ የሚናገር መጥፋቱን፤ ከኮሚቴው አባላት አንዱ የነበሩት ሀዲስ ዓለማየሁ ግን “የመጣው ይምጣ እንጂ እውነቱን እናገራለሁ” ብለው በመወሰን አሥራ ሶስት ገጽ ያለው ማስታወሻ ጽፈው፣ ለንጉሱ በእጃቸው መስጠታቸውን አስነብበን፤ በሕገ መንግስቱና በፓርላማው ያለው ክፍተት፣ የባለሥልጣናቱ ዋልጌነት፣ በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ምሬት ወዘተ በመጠኑ ማሳየታችን ይታወሣል፡፡ ዛሬም የተወሰኑትን አንኳር ጉዳዮች እናካፍላችኋለን፡፡

“በፖለቲካ የኢትዮጵያ ህዝብ የምንለው ከአማራ፣ ከትግሬ፣ ከኦሮሞና ከሌሎችም ልዩ ልዩ ቋንቋ፣ ልማድ፣ ዘር ወይም ሃይማኖት ካላቸው ክፍሎች አንድ ላይ ሆኖ በኢትዮጵያ ዘውድ ስር የሚተዳደረው ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ልዩ ልዩ ቋንቋ፣ ልማድ፣ ዘር ወይም ሃይማኖት ያላቸው ክፍሎች ምንም እንኳ ባንድ ላይ “የኢትዮጵያ ሕዝብ” የሚል ስም ቢሰጣቸውና ባንድ ዘውድ ሥር ቢተዳደሩ፣ በደስታም ይሁን በመከራ፣ በመልካም ይሁን በክፉ ጊዜ አንድ ላይ የሚያስተሳስረውና ህዝብን አንድ የሚያሰኘው የሕብረት ማሰሪያ ያላቸው ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ “በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክፍሎች የሚኖሩ ሕዝቦች በቋንቋ፣ በልማድ፣ በዘርና በሃይማኖት እንደመለያየታቸው መጠን የሕይወት ዓላማቸውም የተለያየ ነው፡፡ ከመሐከላቸው አንዳንዶቹ ከሁሉም የበላይነት ስሜት የሚሰማቸውና ይህ የበላይነት እንዲሁ እንዳለ እንዲኖር የሚመኙ ናቸው። ሌሎቹ የበላይ ነን ከሚሉት ባንበልጥ አናንስም የማለት ስሜት የሚሰማቸውና ይህንኑ ለማረጋገጥ አጋጣሚ ጊዜ ለማግኘት የሚመኙ ናቸው፡፡

ሶስተኛ፤ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸውና የበላይ ነን የሚሉትን ክፍሎች ኃይል ሰብሮ ነጻ የሚያወጣቸው ከፉ ቀን እንዲመጣ የሚጠብቁና የሚመኙ ናቸው” ብለው ነበር ሀዲስ በ “ማስታወሻ” ቸው፡፡ ሀዲስ በ1953 ዓ.ም የነበረው የኢትዮጵያ እውነታ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ምን ስሜት እንደነበረው በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች መድበው አሳይተውናል፡፡ እነሱም፡- የሁሉም የበላይ ነን የሚሉና ይኸው የበላይነታቸው ለዘለዓለም ተጠብቆላቸው መኖር የሚሹ ለዚሁም በቁርጠኝነት የሚታገሉ፣ “የሁሉም የበላይ ነን” ከሚሉት “ባንበልጥ አናንስም” የሚሉና ለዚሁ ዓላማቸው ሰኬትም አንገታቸውን ደፍተው አጋጣሚ የሚጠብቁ፣ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸውና “የበላይ ነን” የሚሉትን ኃይል ሰብሮ ነጻ የሚያወጣቸው ክፉ ቀን እንዲመጣ የሚመኙ እንደነበሩ አስረድተውናል፡፡ ትልቁ ጥያቄ እዚህ ላይ ነው፡፡

ሊነሳ የሚችለው ሀዲስ ዓለማየሁ አሁን ቢኖር ኖሮ የኢትዮጵያን ሕዝብ በስንት ሊከፍሉት ይችሉ ነበር? ያኔ የሁሉም የበላይ ነን የሚሉትስ ዛሬም የበላይነታቸውን እንዳስጠበቁ ናቸው ወይስ በተራቸው የበታቾች ሆነዋል? “ባንበልጥ አናንስም” የሚሉትና አጋጣሚ ሲጠብቁ የነበሩት ተሳክቶላቸው በተራቸው የበላይ ሆነው ይህንኑ የበላይነታቸውን ለዘለዓለም አስጠብቀው ለመኖር እየታገሉ ነው? የበታችነት ስሜት ይሰማቸው የነበሩና ከዚሁ የበታችነት ስሜት ነጻ የሚያወጣቸው ክፉ ቀን ሲመኙ የኖሩትስ ተሳክቶላቸው ነጻ ወጡ? ወይስ ከትንሽነትም በታች ወርደው እንደሰናፍጭ ቅንጣት ይበልጥ ደቀቁ? ሀዲስ ዓለማየሁ ከላይ የተገለጹትን የህብረተሰብ ክፍሎች ሁኔታ ሲያብራሩም “የሕይወት ዓላማቸው የተለያየ ክፍሎች “የኢትዮጵያ ሕዝብ” ከሚለው ስምና ከንጉሰ ነገሥቱ መንግስት የጦር ኃይል በቀር ሌላ የሚያስተባብሩዋቸውና አንድ ላይ የሚያስተሳስሩዋቸው የፖለቲካ ድርጅቶች /Political Institutions/ ስለሚጐድሏቸው በእውነተኛው የፖለቲካ ትርጉም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው ለማለትና ወደ ከፍተኛው የፖለቲካ ደረጃ ደርሷል ወይም በፖለቲካ የበሰለ ነው ለማለት ያስቸግራል” ብለዋል ለንጉሱ በጻፉት ማስታወሻ፡፡ ሀዲስ ልክ የዛሬ 53 ዓመት የተመኙትና ኢትዮጵያን አንድ አርገው ሊመሩ የሚችሉ የፖለቲካ ፖርቲዎች ዛሬስ በሀገራችን አሉ? ይህ ተገቢም ዓቢይም ጥያቄ ይመስለኛል፡፡

እርግጥ ነው በስም ደረጃ ሀገራችን በፖርቲዎች ራሲን ችላለች ግን ብዙዎቹ የጽዋ ማህበር ያህል እንኳ ጥንካሬ የላቸውም፡፡ ዓላማቸውም የኢትዮጵያን ህዝብ አንድ ከማድረግ ይልቅ መንደርተኝነትን የሚሰብክ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ተዋልዶ፣ ተዋዶ እና ተዋሕዶ የነበረው የሀገራችን ህዝብ የጐሪጥ እንዲተያይ፣ እንደ ቆሰለ ጅብ እርስ በራሱ እየተጠራጠረና እየተፈራራ እንዲኖር ሆኗል፡፡ ግሮሰሪዎች፣ ካፌዎችና የምግብ አዳራሾች ሳይቀሩ በጐሳ የተደራጁ መስለዋል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የንግድ ተቋማትን ሳይቀር የጠባቦችና ዘረኞች መናኸሪያ አድርገዋቸዋል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች እኩይ ድርጊት መንደርተኛነት ነግሶ ኢትዮጵያዊነት ኮስሷል፤ እናም የሀዲስ ምኞት ከንቱ ሆኗል ማለት ነው፡፡ የሀዲስ ምኞት እውን እንዲሆን ካስፈለገ፣ እንደ አሜሪካና እንደ ሌሎች በአስተሳሰብም በሀብትም እንደበለጸጉ አገሮች ህብረ ብሄራዊ ፖርቲዎች ያስፈልጉናል፤ ከመንደርተኝነት ወጥተው ህዝቡንም በአገራዊ ስሜት አስተባብረው ወደ ላቀ ደረጀ ማሸጋገር የሚችሉ ፓርቲዎች እንሻለን። በሁለት ዓበይት አጋጣሚዎች እንዳየነው፤ ህዝቡ መንደርተኝነትን የሚያናፍሱለትን ሳይሆን አገራዊ ጉዳዮችን የሚያነሱለትን መሪዎች ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል፡፡ ይህንን ደግም በ1990 ዓ.ም ሻዕቢያ ወረራ የፈጸመብን ጊዜ እንዲሁም በ2003 ዓ.ም የዓባይ ግድብ ሲጀመር ያሳየው አስደናቂ ርብርብ ለፖለቲከኞች ትምህርት የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡

ህዝቡ የመንደር ፖለቲካ አስጠልቶታል፣ አገራዊ ጉዳዮችን አጥብቆ ይሻል፤ የአንድ ፓርቲና የግለሰብ አገዛዝ ፋይዳ የለሽ መሆኑን አሳምሮ ስለሚያውቅ የመሪዎች የስልጣን ዘመን በህግ የተገደበ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ መድበለ ፓርቲ ስርዓት ጠቃሚ ቢሆንም እንደኛ አገር በመንደር የታጠሩ ፓርቲዎች መዘዛቸው ቀላል አለመሆኑንም ህዝቡ አስቀድሞ ያውቃል፡፡ ሀሣብን በነጻ የመግለጽ መብትን በተመለከተም ሀዲስ እንዲህ ብለው ነበር “ሰው በተፈጥሮ ለተከለከለ ነገር ረሃቡ የጸና ስለሆነ መንግስትን ማመስገን ካልሆነ መንቀፍ ክልል ነው የሚባለው ወሬ የገነነ በመሆኑ፣ በየአካባቢውና በየጓዳው መንቀፉና ማማቱ እንዳለ ሆኖ እንደ ተጨቆነ ወይም እንደ ታፈነ ቆጥሮታል። ከዚህም ሌላ መንግስት የአሠራሩ ጉድለት በጋዜጣ ወይም በጉባኤ በገሃድ እንዳይገለጽ መከልከል ብቻ ሳይሆን በስውር የሚያሙትንና የሚወቅሱትንም በሰላይ ይከታተላቸዋል የሚል እምነት ስለተስፋፋ በየአካባቢው የጭቆናና የመታፈን ስሜት ብቻ ሳይሆን የማማረር ድምጽ መሰማት ከጀመረ ቆይቷል” አዎ ህዝብ ደስታውን፣ ብሶቱን፣ ምሬቱንና ድጋፉን የሚገልጽበት አንደበት ያስፈልገዋል፤ አንደበቱ ደግሞ በትክክለኛ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ፤ ሳይጨምር፣ ወይም ሳይቀንስ የሆነውን፣ የተደረገውን ብቻ የሚዘግብ የህዝብ መገናኛ ዘዴ ነው፡፡

የህዝብ መገናኛ ዘዴ /ሬዲዮ፣ ጋዜጣ፣ ቴሌቪዥን ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል) ከመንግስት ቁጥጥር እና ዕዝ ነፃ መውጣት አለበት፡፡ ቁጥጥሩ ሲበዛ፣ ሸምቆቆው ሲጠብቅ መገናኛ ብዙኃን ይቀጭጫሉ፤ ህዝብ የመረጃ ረሃብተኛ ይሆናል፤ በአንጻሩ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን የተጠሉ ይሆናሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ህዝቡ ወደ ተራ ሃሜት ይዞራል፣ ለአገራዊ ጉዳዮችም ጀርባውን ይሰጣል፤ አንድነቱም ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ መንግስት የፈለገውን ያህል እውነት ቢናገርም የህዝቡን አመኔታ ማግኘት ይሳነዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለህዝቡ በተለይ ለመንግስት ትልቅ ፈተና ነው፡፡ መንግስት ኘሮፌሽናል ጋዜጠኞች እንጂ ካድሬዎች ሊጠቅሙት እንደማይችሉ መገንዘብ አለበት “ሀኪም ሲበዛ በሽተኛው ይሞታል” እንደሚባለው የካድሬ ብዛት ሳይሆን የባለሙያዎች ቁጥር መጨመር ነው የሚጠቅመው፡፡ መንግስት የሚያስፈልገው ፖሊሲዎቹን፣ ኘሮግራሞቹንና የልማት ዕቅዶቹን በአግባቡ ተረድተው የሚያብራሩለት፣ የሚተነትኑለትና የሚያስገነዝቡለት ብቁ ጋዜጠኞች እንጂ እሱ ያለውን የሚደግሙለት በቀቀኖች አይደሉም፡፡ በሌላም በኩል ሰላማዊ ሰልፍ ተከለከልን፣ አዳራሽ እንዳንከራይ ተደርገናል ….” የሚሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጩኸት በየጊዜው እንሰማለን፤ ለምን? ቀድሞ ነገር ፓርቲዎች መኖራቸው የሚፈለግ ከሆነ ሰላማዊ ሰልፍ እና የአዳራሽ ውይይት ቢያደርጉ ምንድነው ጉዳቱ? ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ የማይፈቀድ ከሆነ፣ አዳራሽ እንዳይከራዩም /ቢቻል በመንግስት አዳራሾች በነጻ ሊሰበሰቡ ይገባል/ የማይፈቀድ ከሆነ የመድበለ ፓርቲ ማቋቋሚያ ህጉን መሰረዝ የሚሻል ይመስለኛል፤ አለዚያ “ስጋ ሰጥቶ ቢላዋ እንደመከልከል” ይቆጠራል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚባሉትም የሰከነ፣ በእውቀት የሚመራ፣ የሕዝብን እውነተኛ ችግር ሊገነዘብ የሚችልና ይህንኑ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ሊኖራቸው ይገባል። እንዲህ ሲሆኑ በርካታ ተከታይ ለማፍራት ዕድሉን ያገኛሉ፤ መንግስትንም ከስህተቱ ማረም ይችላሉ፡፡

አለዚያ በሰላማዊ ሰልፍ ሰበብ ያለ በቂ ዕቅድ በየጐዳናው ላይ ህዝብን ይዞ ሲዞሩ መዋል እርባና ያለው አይመስለኝም። ለማንኛውም ሀዲስ መፍትሔ ያሉትን ሁሉ ለንጉሱ በድፍረትና መሪር ከረር ባሉ ቃላት አስረዱ፤ ግን ሰሚ አላገኙም ነበር፡፡ ይህ በመሆኑ ለሀዲስ ማስታወሻ መጻፍ ምክንያት የሆኑትና የአመጹ መሪ የነበሩት ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ሞት ሲፈረድባቸው ችሎት ላይ “.… ከእናንተ ከዳኞችና የሞት ፍርድ እንድትበይኑብኝ ካዘዛችሁ ሰው ይልቅ ፍርድ ተቀባዩ የዛሬው ወንጀለኛ የነገው ባለ ታሪክ ነኝ፡፡ የእኔ ከጓደኞቼ መካከል ለጊዜው በሕይወት መቆየትና ለእናንተ ፍርድ መብቃት የዘመኑን ፍርድ ለመጪው ትውልድ የሚያሳይ ይሆናል፡፡ “.. ዋ ! ዋ! ዋ! ለእናንተና ለገዥአችሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃሣቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚደርስባችሁ መዓት የሚያሰቅቅ ይሆናል” ያሉት ሁሉ ከ13 ዓመት በኋላ ደረሰና ንጉሱም ሆኑ የሥርዓቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ፍጻሜ ዘግናኝ ሆነ፡፡ በግብጽ፣ በሊቢያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሆነው እውነትም ይኸው ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን!

Published in ህብረተሰብ
Sunday, 19 January 2014 00:00

የአለም ዕዝነት

          ስለ አላህ መልእክተኛ አንዳንድ ነጥቦችን ለመግለጽ ዕድል በማግኘቴ ከፍተኛ ክብርና ደስታ ይሰማኛል፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ ለአለም እዝነትና ብርሐን ሆነው ስለተላኩት የነብያት መደምደምያ ስለሆኑት ነብዩ መሐመድ (ሰ.አ.ወ) መግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም ያቅሜን ያህል ሞክርያለሁ፡፡ ከአካላዊ ገጽታቸው ልጀምር፡፡ የአላህ መልዕክተኛ ወደር አይገኝላቸውም፡፡ ገጽታቸው ውብ፣ ባህሪያቸው ያማረ ነበር፡፡ በርግጥ መልክና ፀባያቸውን በተሟላ መልኩ ማስቀመጥ ይከብደናል፡፡ ኢማም ቁርጡቢ እንዲህ ብለዋል:- “የአላህ መልዕክተኛ ውበት በተሟላ መልኩ አልተገለፀም፤ ምክንያቱም ውበትን ሁሉ ያካተተ ማንነታቸው በተሟላ መልኩ ቢገለጽ ኖሮ ሶሖቦች (ባልደረቦቻቸው) ገጽታቸውን ለማየት አቅም አይኖራቸውም ነበር፡፡ ሶሖቦች የአላህ መልክተኛ ዘወትር አብረዋቸው ቢሆኑም ከአናሳ ግብራቸው የተነሳ የመልእክተኛውን ውበት ብርሐን እስኪጠግቡ ያዩት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ አቡበከርና ዑመር ባሉበት የአንሷሮችና የሙሐጂሮች ስብስብ ነብዩ መሐመድ ሲመጡ ከአቡበከርና ከዑመር በስተቀር ሌሎች ሶሖቦች አንገታቸውን አቅንተው ሊያዩአቸው አይደፍሩም ነበር፡፡

ሁለቱ ግን ያዩአቸዋል፡፡ ፈገግታም ይለዋወጣሉ፡፡ (ቲርሚዚ) ግብጽን ያቀናው አሚር ቢን አልአስ በዕድሜው መጨረሻ ላይ ስለዚህ ነገር ሲያወጋ እንዲህ ብሏል:- “ከአላህ መልዕክተኛ ይበልጥ ተወዳጅና የተከበረ ሰው ከኔ ዘንድ አልነበረም፡፡ ለርሳቸው ካለኝ ክብር የተነሳ አይኔን ሞልቼ ላያቸው አልደፍርም፤ ገጽታቸውን እንዳብራራ ብጠየቅ እንኳን ይህን ማድረግ አልችልም፡፡ (ሙስሊም) የተባረከው የነብዩ ፊት በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች የስክነትና የመረጋጋት መንፈስ የሚያሰፍን እጅግ ውብና ንፁሕ ገጽታ ነበረው፡፡ ከአይሁድ የሐይማኖት ሊቃውንት መካከል አንዱ የነበረው አብደላህ ቢን ሰላም፤ እስልምናን ከመቀበሉ በፊት የስደት ሐገር ከሆነችው መዲና እንደደረሰ የነብዩን፣ የተባረከ ፊት ባየ ጊዜ እንዲህ ለማለት ተገዷል:- “ይህ ፊት የሐሰተኛ ሰው ፊት አይደለም” (ቲርሚዚ ቢን ማጂህና አህመድ) የነብዩ ውበት፣ ግርማ ሞገስና የገጽታቸው ብርሐን ነብይነታቸውን የሚመሰክር ከመሆኑ የተነሳ የአላህ መልዕክተኛ ለመሆናቸው ሌላ ዋቤ ወይም ተዐምር አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ ገጽታቸው፤ ትህትናን፣ ቆራጥነትን፣ ጽናትን እንዲሁም የላቀ አላማ የተሸከመ ህያው ነበር፡፡ የአዛኝነታቸውን ጥልቀት ለመግለጽማ ያስቸግራል፡፡ ነብዩ (ሰ.ወ) ፊታቸው የውበት ቋት ነበር። ንግግራቸው ይመስጣል፡፡

ገለጻቸው ያፈዛል። አንደበታቸው ርቱዕ ነው፡፡ አማረመዳቸው ይማርካል፡፡ ንግግራቸው ምክርና ጥበብ ብቻ ነበር። አሉባልታና ፍሬ አልባ ወግ አያውቁም፡፡ ትሁትና ልዝብ ነበሩ፡፡ ተንከትክተው አይስቁም፡፡ ሳቃቸው ፈገግታ ነበር፡፡ በድንገት ያያቸው ልቡ በፍርሃትና በአክብሮት ይመላል፡፡ የተላመዳቸው ደግሞ ከልቡ ይወዳቸዋል፡፡ ቸርነታቸው ሊገለጽ ከሚችለው በላይ የበዛ ነበር፡፡ ጂቢር እንዲህ ሲሉ ይህን ዕውነታ ገልፀዋል። “የአላህ መልክተኛ አንዳች ነገር ተጠይቀው አይከለከሉም ነበር፡፡ (ሙስሊም) ንግግራቸው እውነተኛ ነው፡፡ ሲበዛ ብልህ ናቸው፡፡ በጥልቀትና በተከታታይ ያስባሉ፡፡ ዝምታቸው ረጅም ነው፡፡ ሲናገሩ ንግግርን ይሞላሉ። በጥቂት ቃላት ብዙ መልእክት የማስተላለፍ ክህሎት ነበራቸው፡፡ የአላህ መልዕክተኛ የጐረቤትን ሐቅ በመጠበቅ በኩል በጣም ጉጉ ነበሩ፡፡ እንዲህ ሲሉም ተናግረዋል:- “ጅብሪል (ገብርኤል) ስለጐረቤት የውርስ ባለመብት ያደርገዋል ብዬ እስካስብ ድረስ ኑዛዜ አስተላለፈልኝ፡፡ የጐረቤት መብት መጋፋት በብዙ መልኩ ይገለጻል፡፡ ለምሳሌ አጮልቆ ሚስጥሩን መመልከት፣ በምግብ ሽታ ማወክ፣ የማይወደውን ድርጊት መፈፀም፡፡” ይህም በመሆኑ የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል:- “ከአላህ ዘንድ መልካሙ ባልንጀራ፤ ለባልንጀራው መልካም የሆነው ነው፡፡

መልካሙ ጐረቤት ለጐረቤቱ መልካም የሆነው ነው፡፡ (ተርሚዚኑ) የአላህ መልዕክተኛ እዝነት፤ ለጦር ምርኮኞች ሳይቀር ተትረፍርፎአል፡፡ የሙስአብ ቢን ዑመይር ወንድም አቡ ዐዚዝ እንዲህ ሲል አውግቷል፤ “ከበድር ምርኮኞች አንዱ ነበርኩ፡፡ የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ የሚል ትዕዛዝ አስተላለፉ:- “ምርኮኞችን በበጐ ሁኔታ ትይዙ ዘንድ አደራ እላችኋለሁ፡፡” የአላህ መልዕክተኛ ከርሳቸው መምጣት በፊት በአለም ላይ ሰፍኖ የነበረውን የባርያ አሳዳሪ ስርዓት በሂደትና ደረጃ በደረጃ የማስወገድ እርምጃዎችን መውሰዳቸው ይታወቃል፡፡ ሰዎች ባሮቻቸውን ነጻ ይለቁ ዘንድ በየአጋጣሚው ያበረታቱ ነበር፡፡ ባርያን ነጻ መልቀቅ ትልቅ ዒባዳ (አላህን መፍራት) መሆኑን አስተምረዋል፡፡ በመሆኑም የነብዩ የቅርብ ወዳጅ አቡበከር፤ አብዛኛውን ገንዘባቸውን ያዋሉት ባሮችን እየገዙ ነጻ ለመልቀቅ ተግባር ነበር፡፡ መዕሩር ቢን ሰወይድ እንዲህ ሲሉ አውግተዋል:- “አቡዘርን በረበዛህ ውስጥ አገኘኋቸው። የሚያምር ልብስ ለብሰዋል፡፡ አገልጋያቸውም ተመሳሳይ ልብስ ለብሰዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ጠየቅኳቸው፡፡ ተከታዩን ነገሩኝ፡፡ “አንድን ሰው ተሳደብኩ፡፡ እናቱን አስነወርኩበት፡፡ ነብዩም እንዲህ አሉኝ፡፡ “አቡ ዘር ሆይ፤ እናቱን ማነወርህ ተገቢ አይደለም፡፡ የጀህልያ ቅሪት ያለብህ ሰው ነህ። አልጋዮቻችሁ ወንድሞቻችሁ ናቸው፡፡

አላህ ወንድሙን ከስሩ ያደረገለት ሰው ከሚመገበው ይመግበው፡፡ ከሚለብሰው ያልብሰው፡፡ የማይችሉትንም ስራ አትዘዟቸው፡፡ ካዘዛችኋቸውም እርዷቸው፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም) በጀህሊያ ዘመን (በድንቁርና ዘመን) ሴቶች ክብር አልባ አያያዝ ይያዙ ነበር፡፡ የጀህሊያ ሰዎች ሴቶቻቸውን ያለርህራሄ ከነህይወታቸው ይቀብሩ ነበር፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚደርስባቸውን መነወርንና ውግዘትን በመፍራት ነበር፡፡ ከአለት የጠጠረ ልባቸው ይህን ወንጀል ምንም ሳይመስለው ይፈጽማል፡፡ እንስት ስትወለድ ይሰማቸው የነበረውን የሐፍረት ስሜት አላህ እንዲህ በማለት በቁርዓን ውስጥ ገልጾታል:- “ከእነርሱ መካከል አንዱ በሴት ልጅ በተሰበረ ጊዜ ፊቱ በሐዘን ይጠቁራል፤ ቅስሙ ይሰበራል (አል - ነህል 58) በጀህልያ ዘመን ሴቶች ደረጃቸው ዝቅ ብሎ፣ ክብራቸው ተነክቶ፣ የሴሰኝነት ፍላጐት መወጫ ብቻ ነበሩ፡፡ ነብዩ እንዲህ ብለዋል:- ጀነት (ገነት) ከእናቶች እግር ስር ትገኛለች (አልነሳኢ) የአላህ መልዕክተኛ በጉዞ ላይ ነበሩ፡፡ አንጀሿህ የተባለ አገልጋያቸው አብሯቸው ነበር። የአላህ መልዕክተኛ በግመሎቹ ላይ የተሳፈሩ ሴቶች እንዳይንገላቱ ስጋት ገባቸው፡፡ ስለዚህ አገልጋያቸውን እንዲህ አሉት:- “አንጀሻህ ሆይ፤ ረጋ በል፤ ለነዚህ ስስ ብርጭቆዎች እዘንላቸው (በኻሪና አህመድ) በሌላ ሐዲስ እንዲህ ብለዋል፡፡

“ከዱንያ ውስጥ ሁለት ነገሮች ከኔ ዘንድ የበለጠ ተወዳጅ ሆኗል፡፡ እነርሱም ሴትና ሽቶ ናቸው፡፡ ሶላት የአይኔ ማረፊያ ተደርጋለች” (ነሣኢና አሕመድ) “ሶስት ሴት ልጆች ወይም ሶስት እህቶች እንደዚሁም ሁለት ሴት ልጆች ወይም ሁለት እህቶች ኖረውት ተንከባክቦ ያሳደጋቸው፣ በነርሱ ጉዳይም አላህን የፈራ ጀነትን ያገኛል” ያሉት እኝህ ታላቅ ነብይ ናቸው፡፡ (ቲርሚዙ አቡ ዳውድና አህመድ) “ሁለት ሴት ልጆችን ለአካለ መጠን እስኪደርሱ ድረስ ተንከባክቦ ያሳደገ፣ እኔና እርሱ ጀነት ውስጥ እንደዚህ እንሆናለን” ብለዋል ጣቶቻቸውን አጠጋግተው እያሳዩ (ሙስሊምና ተርሚዝያ) የጀህሊያ ሰዎች ለእንስሳት አያዝኑም ነበር። በመጥፎ አያያዝ ይይዟቸዋል፡፡እንስሳትን እርስ በእርስ እያዋጉ እና እያጋደሉ ይዝናናሉ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ይህንን ድርጊት በመቃወም ከለከሉ፡፡ አቡ ዋቂድ ለይሲ እንዲህ ሲል አውግቷል:- “የመዲና ሰዎች የግመል ሻኛና የፍየል ላት ይወዱ ነበር፡፡ ከነህይወታቸው እየቆረጡ ይመገብዋቸው ነበር፡፡ የአላህ መልክተኛ ግን ይህንን ድርጊት እንዲህ በማለት ከለከሉ:- “እንስሳት በህይወት እያሉ ከአካላቸው የሚቆረጥ ስጋ ሁሉ በክት ነው (ተርሚዝይ አህመድ) ጆቢር እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ ፊቱ የተጠበሰ አንድ አህያ ተመለከቱና እንዲህ አሉ:- “ይህን ድርጊት አልከለከልኳችሁም ነበርን? ይህን የፈጸመውን ሰው አላህ ረገመው፡፡” የአላህ መልዕክተኛ መካን ለመቆጣጠር አስር ሺህ ሰራዊት ይዘው በዘመቱ ጊዜ መንገድ ላይ አንዲት እናት ውሻ፤ ተንጋላ ልጆችዋን ስታጠባ ተመለከቱ፡፡

እርሷንም ሆነ ልጆችዋን ወታደሮች እንዳያውኳቸው ይከለከል ዘንድ አንድ ሶሐባቸውን (ባልደረባቸውን) አዘዙት፡፡ (አልዋቂዲ) “አንደበት በሌላቸው እንስሳዎች ጉዳይ አላህን ፍሩ፡፡ በመልካም አያያዝ ጋልቧቸው፡፡ በመልካም አያያዝም ተመገብዋቸው (አቡ ዳውድ) ነብዩ መሐመድ (ሰ.አ.ወ) ከማረፋቸው በፊት የተናገሩትን ንግግር ቀንጨብ አድርጌ አቀርበዋለሁ። እጀምረዋለሁ እንጂ አልጨርሰውም፡፡ ምክንያቱም በቂ ጊዜና ቦታ ስለሌለኝ፡፡ “እናንተ ሰዎች ሆይ፤ ንግግሬን አድምጡ፡፡ በዚህ ቦታ በተከታዩ አመት በምንም መልኩ ላንገናኝ እንችላለን፡፡ እናንተ ሰዎች ሆይ፤ አላህን እስክታገኙ ድረስ ይህ ቀንና ወር ብሩክ እንደሆነ ሁሉ ደማችሁና ገንዘባችሁም የተከበረ ነው፡፡ ፈጣሪያችሁን መገናኘታችሁ አይቀርም፡፡ የሰራችሁትን ድፍረትም ይጠይቃችኋል፡፡ በበኩሌ መልክቴን አድርሻለሁ። አደራ ያለበት ሰው ለባለንብረቱ ይመልስ፡፡ ወለድ (አራጣ) ውድቅ ነው፡፡ ግና ዋናው ገንዘባችሁ ወረታችሁ የናንተው ነው፡፡ አትበደሉም፤ አትበድሉም” ነብዩ መሐመድ (ሰ.አ.ወ) ያረፉ እለት የቅርብ ባልደረባቸውና ከሳቸውም በኋላ ኻሊፋ ሆነው የተሾሙት አቡበከር አልሰደቅ፤ ሰውን ሁሉ ሰብስበው እውነተኛው ነብይ ህይወታቸውን በሙሉ ያስተማሩትን ትምህርት እንዲህ ሲሉ ደግመውታል። “እናንተ ሰዎች ሆይ፤ መሐመድን ታመልኩ ከነበር መሐመድ ይሄው ሞቷል፡፡ አላህን የምታመልኩ ከሆነ ግን እሱ አይሞትም፡፡ ዘላለማዊ ነው፡፡”

Published in ህብረተሰብ
Sunday, 19 January 2014 00:00

ጥምቀት በአዲስ አበባ

ከ123 አብያተ ክርስትያን የሚወጡ ታቦታት በ46 ጥምቀተ ባሕሮች ያድራሉ

በየዓመቱ በኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በሀገሪቱ ውስጥ በጐዳናና በአደባባይ ከሚከናወኑ በዓላት አንዱ ነው፡፡ አንዲት የውጭ ሀገር ዜጋ በአንድ ዘመን ይህን በዓል ከተመለከተች በኋላ፤ “በየትኛውም ሀገር የሚከበር ካርኒቫል የማይተካከለው፣” ስትል አድንቃ ጽፋለች። ይቺ ጸሓፊ በብራዚል ዘመን መለወጫ ላይ የሚፈፀመውን ካርኒቫል ጭምር በመጥቀስ ነበር የጥምቀቱን አቻ የለሽነት የገለጠችው፡፡ አውሮጳዊቷ ጥምቀትን የተመለከተችው አዲስ አበባ ላይ ነበር፡፡ የጥምቀትን በዓል የደመቀና ቀለማም የሚያደርገው ከአከባበሩ ሥነሥርዓት ጋር በዓሉ የሚከናወንበት ቦታም የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። በከተማና በገጠር ያለው አከባበር ሥነ ሥርዓት አንድ ቢሆንም በድምቀቱ ይለያያል፡፡ ይህም ማለት በከተማ ውስጥ ብዙ ሕዝብና ብዙ ታቦታት በመኖራቸው ነው፡፡ “አርባ ዓራቱ ታቦት” የሚል የተሳሳተ ጥሪ የፈጠረው የጐንደሩ ጥምቀት፣ በነገሥታቱዋ ዘመን በጐንደር የነበሩት ፵፬ አድባራት በአንድነት ወጥተው፣ በነገሥታቱ የመዋኛ ቦታ ተሰብስበው እጅግ ልዩ ድምቀትና የበዙ ቀለሞችን ስለሚፈጥሩበት ነው፡፡ እንደዚህ ሲታይ ነው ጥምቀት በአዲስ አበባ እጅግ ልዩ ኾኖ የሚገኘው፡፡

በየትኛውም የሀገሪቱ ከተሞች ጥምቀት የሚከበረው በአንድ ቦታ ሲኾን በአዲስ አበባ ውስጥ ግን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ነው፡፡ የሚያስገርም ነው:- ጥምቀት አዲስ አበባ በሚባለው ክልል ውስጥ በ46 የጥምቀት ባሕሮች ላይ ይከበራል! በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ ከ120 በላይ የሚኾኑ አብያተ ክርስትያኖች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቤተክህነት ባገኘነው የዘንድሮ የጥምቀት በዓል አከባበር መርሐ ግብር ዝርዝር መሠረት፤ 123 አብያተ ክርስትያን ወደተለያዩ ቦታዎች ታቦታቶቻቸውን ይዘው ይወጣሉ፤ ይመለሳሉ፡፡ መንገዶች ኹሉ ወደ ጥምቀተ ባሕሮች በሚሔዱ፣ ከጥምቀተ ባሕሩም ወደየቤታቸው በሚመለሱ ታቦታት እና እነሱን አጅቦ በሚከተል ጥምቀትን አክባሪ ምዕመናን፣ ከከተራ ጀምሮ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ የተሞላ ይኾናል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎችም አራተኛ ቀኑን (ጥር 13) ይጨምራል፡፡ ከእያንዳንዱ ቤተክርስትያን በትንሹ ሁለት ታቦታት መውጣታቸው አይቀርም፡፡ በድምሩ ከሁለት መቶ ሃምሳ ያላነሱ ታቦታት፤ ዛሬ ጥር 10 ቀን ከየአድባራቱ በመውጣት ወደ 46ቱ ጥምቀተ ባሕሮች ይወርዳሉ፡፡

ከነዚህ የአዲስ አበባ ባሕረ ጥምቀቶች ውስጥ 15ቱ ብቻ ናቸው የአንድ አንድ ቤተክርስትያን ታቦቶች ማደሪያና ጥምቀትን ማክበሪያ የሚሆኑት። ሁለት ሁለት ቤተክርስትያኖች የሚያከብሩባቸው 12 ጥምቀተ ባሕሮች ያሉ ሲሆን፣ የሦስት ሦስት አብያተ ክርስትያን ታቦታት የሚያድሩባቸው ደግሞ 7 ባሕረ ጥምቀቶች ናቸው፡፡ በአምስት ባሕረ ጥምቀቶች አራት አራት ቤተክርስትያኖች እንደሚያድሩም ከቤተክሕነቱ ዝርዝር ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ስሌት፣ አምስት አምስት አብያተ ክርስትያናት ጥምቀትን የሚያከብሩባቸው አራት ባሕረጥምቀቶች ሲኖሩ፣ ከቀሩት ሦስት ባሕረ ጥምቀቶች ሁለቱ፤ ከስድስት እና ከሰባት አድባራት የሚወጡ፤ አንዱ ደግሞ ከአስር አድባራት በሚወጡ ታቦታትና ምዕመናን በድምቀት የሚከበርበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የጃንሜዳው ጥምቀተ ባሕር፣ ከዚህ በፊት የ11 አብያተ ክርስትያናት ጥምቀት ማክበሪያ እንደነበረ የሚታወቅ ቢኾንም፣ በዘንድሮው ዝርዝር ላይ ለማረጋገጥ የተቻለው በጥምቀተ ባሕሩ የሚያድሩት ከ10 አድባራት የሚወጡ ታቦታት እንደሆኑ ነው። ምናልባት እንደምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ያለውንም በመቁጠር ይሆናል 11 ሲባል የቆየው ያስብላል፡፡ ስደተኛው በመባል የሚታወቀው የምስካየኅዙናን መድኃኔዓለም ግን ለጥምቀትም ታቦቱ ከቤተክርስትያኑ የማይወጣበት ሥርዓት ካላቸው ገዳማት አንዱ ነው፡፡ በጃንሜዳው የሚያድሩ ታቦታት ከታዕካ ነገሥት በዓታ፣ ከመ/ጸ/ቅድስት ሥላሴ፣ ከገነተጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ፣ ከመንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም፣ ከቀጨኔ ደ/ሰ/መድኃኔዓለም፣ ከደ/ነ/ቅ/ዮሐንስ፣ ከመ/ል/ቅ/ማርቆስ፣ ከቀበና መ/ሕ/አ/ገ/መ/ቅዱስ፣ ከገነተ ኢየሱስ እና ከአንቀጸ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሚወጡ ታቦታት ናቸው፡፡ ከጃንሜዳው በመቀጠል ከሰባት አድባራት የሚወጡ ታቦታት፤ ጥምቀትን የሚያከብሩበት ጥምቀተ ባሕር ደግሞ በኮልፌ - ቀራንዮ፣ በትንሹ አቃቂ ወንዝ ላይ በሚገኘው ገዳመ ኢየሱስ ቅጽረ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ቦታ የቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ የደብረ ገሊላ ዓማኑኤል፣ የሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ፣ የገዳመ ኢየሱስ፣ የደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ፣ የወይብላ ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም እና የፊሊዶሮ አቡነተክለሃይማኖት ታቦታት ያድራሉ፡፡

በኮተቤው ወንድይራድ ት/ቤት አጠገብ በሚገኘው ጥምቀተ ባሕር ደግሞ ከ6 አድባራት የሚወጡ ታቦታት ያድራሉ፡፡ በጉለሌው የራስ ኃይሉ ሜዳ፣ በኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 24 ቀበሌ 15፣ በደብረ ዘይት መንገድ ፍሬሕይወት ት/ቤት አጠገብ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 26 ቀበሌ 06 አቃቂ ወንዝ ላይ በሚገኙት ባሕረጥምቀቶች ደግሞ በእያንዳንዳቸው ከአምስት አብያተ ክርስትያናት የሚወጡ ታቦታት ያድራሉ። ከጥምቀት በዓል ቀጥሎ ጥር 12 ቀን በሚከበረው የቃና ዘገሊላ በዓልም በጥምቀተ ባሕሩ ሁለት ሌሊቶችን የሚያድሩት የቅዱስ ሚካኤል አብያተ ክርስትያን ታቦታት ወደየቤተክርስትያናቸው ይመለሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ በቅዱስ ሚካኤል ስም የሚታወቁ 14 አብያተ ክርስትያን አሉ፡፡ እነዚህም በ14 የተለያዩ ጥምቀተ ባሕሮች የሚያድሩ ናቸው። በጃንሜዳ፣ በየካ ወረዳ 16 ቀበሌ 11 ኳስ ሜዳ፣ በኮተቤ ወንድይራድ ት/ቤት፣ በቦሌ ወረዳ 20 ቀበሌ 01፣ በየረር ሠፈራ አካባቢ፣ በጉለሌ ራስ ኃይሉ ሜዳ፣ በቤቴል ኳስ ሜዳ፣ በላይ ዘለቀ መንገድ አዲሱ ገበያ፣ በመንዲዳ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ፣ በመካኒሳ ወረዳ 23 ቀበሌ 04፣ በአፍሪካ አንድነት አካባቢ ወረዳ 23 ፊት ለፊት፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ጨፌ ዳዲ ሜዳ፣ በአቃቂ ወንዝና በቃሊቲ አካባቢ የሚያድሩ የሚካኤል ታቦታት በጥር 12 ነው ወደየቤተክርስትያናቸው የሚመለሱት፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ የሚካኤል ታቦትን በድርብ የያዘው የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስትያን ታቦቶችም በዚሁ እለት ነው ወደቤታቸው የሚመለሱት፡፡ በአዲስ አበባ ከጥምቀት ጋር ተያይዞ የሚከበረው የእግዚአብሔር አብ የንግሥ በዓልም በተመሳሳይ ኹኔታ ታቦታት ወደመንገዶች እና አደባባዮች በመውጣት የሚከበር ነው። በአራተኛው ቀን ጥር 13 በተመሳሳይ ሁኔታ የሚከበርባቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ የደብረ ምጽላል እግዚአብሔርአብ፣ በአዲሱ ገበያ ደብረ ሲና እግዚአብሔርአብና በጉለሌው ጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል ናቸው፡፡ ጥምቀት በአዲስ አበባ በሰሜን ከእንጦጦና ከቃሌ ተራራ ጀምሮ እስከ ደቡብ የቃሊቲ ገጠሮች ድረስ፣ በምዕራብ ከትንሹ አቃቂ ወንዝ እስከ ምሥራቅ ወንድ ይራድ ት/ቤት (ኮተቤ) ድረስ በጐዳናዎች፣ በአደባባዮችና በየማርገጃው ለአራት ቀኖች ያህል እንዲህ ባለ አጀብና ድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ ፀሐፊውን በሚከተሉት የኢ-ሜልና ፌስቡክ አድራሻ ማግኘት ይቻላል ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. / This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

              እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሠላም አደረሳችሁ፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በቃ የአበሻ ልጆች በየሄድንበት ‘ትክሻውን የሚያሳየን’ ይብዛ! ግራ ገባን እኮ… ገሚሶቹ “በህገ ወጥ መንገድ ገብታችሁ…” አሉና አስወጡን፣ ገሚሶቹ ደግሞ…“በህገ ወጥ መንገድ ስለገባችሁ አሽቀንጥረን ልንወረወራችሁ ነው …” እያሉን ነው፡ (ዚምባብዌ አለችበት ነው የተባለው!) ይሄን ሁሉ “የወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል” ብለን ዝም አልን… (“ይሁን ብለን ዝም አልን…” የምትለው የመጽሐፉ ቃል ‘ትመቸኛለች’፡፡) አሁን ደግሞ ያ ሁሉ አልበቃ ብሎ ጭራሽ በህጋዊ ሰነዶች ያውም ‘ዓለም ላወቀው ፀሀይ ለሞቀው ሥራ’ የሚሄዱ ጋዜጠኞችን መከልከል… “ልብ ያለው ልብ ያድርግ” የሚያሰኝ ነው፡፡

ምን ገረመህ አትሉኝም… የስፖርት ጋዜጠኞቹ እንደዛ ሲጉላሉ “ህጋዊ በሆኑ ዜጎቼ ላይማ እንዲህ ማድረግ አትችሉም!” ምናምን የሚል… “የእኔ ጋሻ፣ የእኔ መከታ!” የሚባለው አይነት ኦፊሴላዊ ድምጽ መጥፋቱ፡፡ አሀ…ሳንወድ በግድ “የአህያ ባል…” ምናምን የሚሉት ተረት ትዝ ሊለን ምንም አልቀረማ! እኔ የምለው…እኛ ሰውዬ… “ንቀውናል፣ ደፍረውናል፣ ብታምኑም ባታምኑም በቁማችን ሞተናል!” ምናምን አልነበር ያሉት! ይኸው ከስንት ዘመን በኋላ ንቀቱም፣ ድፍረቱም ቅጥ እያጣ አይመስላችሁም! ነገራችን እኮ…አለ አይደል… “ለመከራ ያለው መነኩሴ ዳዊቱን ሸጦ አህያ ይገዛል” ሆኗል፡፡ ምንም ‘የምንሸጠው ዳዊት’ ባይኖረንም ለመከራ ያለን እየሆንን ነው፡፡ ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… “ተልባ በጥባጯ እያለች ጎመን ቀንጣሿ ምች መታት…” የሚሏት ተረት ትዝ ትላችኋለች? እንዴት አሪፍ አባባል መሰለቻችሁ፡፡

‘ጎመን እየቀነጠስን” ምች የሚመታን በዛና! ይቺን ስሙኝማ…በዛ ሰሞን አንድ ስፍራ ላይ ሁለት ሰዎች በሆነ ነገር ይጋጫሉ፡፡ ገላጋይ ሀይ፣ ሀይ ብሎ እንደምንም ለያይቷቸው እያስማማቸው እያለ፣ የአንደኛው ጓደኛ የተባለ ሰውዬ ይመጣል፡ እናላችሁ… ጉዳዩን ሳያውቅ፣ “በምን ተጋጩ…” እንኳን ብሎ ሳይጠይቅ፣ ዋናው አጥፊ የእሱ ጓደኛ ይሁን፣ አይሁን እንኳን ሳያውቅ ነገሩን እንደ አዲስ ጀመረው፡፡ ዋናው ባለጉዳይ እኮ “ይቅር ለእግዜር እየተባባለ ነው! እናላችሁ…በየቦታው ‘ጎመን ቀንጥሰን ምች የሚመታን’ በ‘ማይኮነስረን’ አቧራ የምናስነሳ መአት ነን፡፡ “ነገር የሚከረው ጎንጓኙን ሲያገኝ ነው” የሚሏት ተረት አለች፡፡ ፈረንጆቹ ሰው በማያገባው ነገር ጥልቅ ሲል…‘ኢትስ ነን ኦፍ ዩር ቢዝነስ’ የሚሏት ኩም ማድረጊያ አባባል አለቻቸው፡፡ እኛ ዘንድ ያለጉዳያችን ‘የምንለጠፍ’፣ ‘አብራችሁ ካልሰፋችሁኝ’ የምንል እየበዛን ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንዴት ነው ባህሪያችን መሽቶ ሲነጋ መቶ ሰማንያ ዲግሪ ተሽከርክሮ ወዲያኛው ጫፍ የሚሄደው! ምን መሰላችሁ…ትናንትና “ኑሮ ከበደን እያልን እየጮህን እርምጃ የማይወስዱት እነኚህ ሰዎች ጭራሽ በምድር ላይ ያለን አይመስላቸውም እንዴ!” ምናምን ስትባባሉ የነበረው ሰውዬ፤ በሦስተኛው ቀን መቶ ሰማንያ ዲግሪ ይሽከረከርና… “ምን አለ በለኝ በጥቂት ዓመት ውስጥ ሦስት ዲጂት ዕድገት ባንገባ…” ምናምን አይነት ነገር ይላችኋል፡፡ ወይ ደግሞ ትናንት ይሄ የባቡር፣ የመንገድ፣ የህንጻ ሥራ ምናምን አሪፍ ነገሮች አይደሉ! አዲስ እኮ ሲንጋፖርን ልትመስል ምንም አልቀራት…” ምናምን ስትባባሉ የቆያችሁት ሰው በሦስተኛው ቀን… “እኔ የምለው እነኚህ ሰዎች መንገዱን ሁሉ ቆፍረው፣ ቆፍረው… ጣልያን የደበቀው ማርትሬዛ አለ ተብለዋል እንዴ!” ምናምን ይልላችኋል፡፡ ግራ ገባን …አይደለም ለወራት ወይም ለዓመት የተለያየው ሰው፣ ሳምንት ቆይተን የምናገኘው ሰውም ‘ሪሳይክልድ’ ምናምን ሆኖ እየመጣ ግራ ገባን! (በዛ በመተሳሰቡ ዘመን ቢሆን… “እኔን ግራ ግብት ይበለኝ! ምነው እንዲህ ሆድ ባሰህ!” የሚል አዛኝ አይጠፋም ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን “ታዲያ አካሄዱን አላውቅበት ብለህ ስትደናበር ግራ ቢገባህ እኛ ምን እናድርግህ! ባወጣ ያውጣህ! አይነት ነገር ሆኗል!) እናላችሁ ‘ጎመን እየቀነጠስን ምች የሚመታን’ ስንበዛ ሁሉም ነገር ‘አርቲፊሻል’ ይሆናል፡፡ የራስ እምነት፣ የራስ ሀሳብ ብሎ ነገር የለም፤ ሀሳብና እምነት አንጻራዊ ናቸው፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) ዋናው ‘ጨዋታ’ ጎመን ቀንጥሰን በምች ለመመታት አዋጪውን መንገድ ማወቁ ሆኗል፡፡

ነገርዬውማ እንግዲህ እንዲህ የሚያደርገን እስከምን ድረስ መሰላችሁ…የሚያዋጣ ገበያ እስኪደርስ! በሥራ አካባቢ በሉት፣ በመኖሪያ አካባቢ በሉት፣ በሌሎች ማህበራዊ …በሉት ጎመን ቀንጥሰን ምች የሚመታን የሌለንበት ቦታ የለም፡፡ ስሙኝማ…ታዋቂ ሰዎች አካባቢ፣ ፈረንካ ያላቸው ሰዎች አካባቢ፣ ወፍራም ላይ የሚቀመጡ ሰዎች አካባቢ የማይጠፉ ‘ባለሟሎችን’ ተመልከቱ…ምን አለፋችሁ “ሰው ይሄን ያህል ይወርዳል!” ያሠኛችኋል፡፡ ሬስቱራንት ውስጥ አሳላፊ ካልመጣ የሚቆጡት ‘ምች የሚመታቸው’ ባለሟሎቹ ናቸው፣ ባለ ወፍራም ወንበሩ ሊፍት ውስጥ ቀድሞ እንዲገባ መንገድ ካልተለቀቀ ‘ምች የሚመታቸው’ ባለሟሎቹ ናቸው፣ ለታዋቂዎቹ ሰዎች ጠብ እርግፍ ካላላችሁ ‘ምች የሚመታቸው’ ባለሟሎቹ ናቸው፡፡ የ‘ቦተሊካ’ ነገሩንማ ተዉት፡፡ “ተልባ በጥባጯ እያለች ጎመን ቀንጣሿ ምች መታት…” ተረት በትክክል የምትሠራው እዚህ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በዚህ ወገን ወይ በዚያ ወገን በመሆናችሁ፣ ወይንም ናችሁ ተብሎ በመታሰቡ ‘የሚወርዱባችሁ’… አለ አይደል… ‘ጎመን ቀንጣሾቹ’ የምች ሰለባዎች ናቸው፣፣ (ቂ…ቂ…ቂ….) እግረ መንገዴን ሀሳብ አለን…እነኚህ የበዙት ‘የፍረጃ’ ስሞች በአንድ ይጠቃለሉልንማ! አሀ…በዛብና! የበፊቱ አሪፍ ነበር፡፡ በቃ ነገራችን ‘አላምር ካለ’…ፀረ አብዮተኛ ይባላል አለቀ፣ ደቀቀ፡፡ እንደ ዘንድሮ… ‘ናፋቂ’ የለ…‘ምናምኒስት’ የለ…‘ኒኦ ምናምን’ የለ… ‘አፍቃሪ ምናምን’ የለ… እና የምንጠራባቸው ‘የፍረጃ ስሞች’ ተጠቃለው አንድ ይሁኑልንማ፡፡ አሀ… ጎመን ቀንጥሰው ምች የሚመታቸው ቃላት መለማመጃ አያድርጉና! እኔ የምለው… “በቀደም ሁሉን አንድዬ ፊት ወስደህ ስታስለፈልፍ ምነው የአንተ ቢጤ ጋዜጠኞችን አልጠቀስክ…” ምናምን ያልከኝ ወዳጄ…ምን መሰለህ የእኛ ነገር ለአንድዬ ለራሱ እንኳን ግራ የሚያጋባ ሆኗል! አሀ…ልክ ነዋ… እንደ ጋዜጠኛ ‘ማህበራት መፍላት’ ከሆነ ብዛታችን እኮ… አለ አይደል… እናላችሁ ጋዜጠኛ አንድዬ ፊት ይቀርባል… “አንተ ደግሞ ምን ነበርክ?” “ጋዜጠኛ…” “ይቅርታ ምን አልከኝ?” “ጋዜጠኛ፡፡

” (አንድዬ ከት ብሎ ይስቃል) “አንድዬ…ምነው ጋዜጠኛ መሆን ይህን ያህል ያስቃል?” “አይ ምን….” (እንደገና ሳቅ ያቋርጠዋል) “ኧረ አንድዬ ስሜቴን እየጎዳህብኝ ነው?” “ይቅርታ የእኔ ልጅ…የእኔ ልጅ ልበልህ እንጂ! ወይ ጋዜጠኛ! አንተን ለብቻህ ነው የማናግርህ?” “ምን አጠፋሁ…” “መጀመሪያ ምን ጋዜጣ ወይም ምን ጣቢያ ላይ ነው የምትሠራው?” “ጌታዬ ጋዜጠኛ ለመባል የግድ ወረቀት ላይ መለቅለቅ ወይም መለፍለፍ አያስፈልገኝም፡፡ ጌታዬ ከፈለግህ የጋዜጠኛ ማህበር አባልነት መታወቂያዬን አሳይሀለሁ፡፡” “እሱ አይደል እኔንስ ግራ የገባኝ… ነው ወይስ ማህበር የምታቋቁሙት እንደ እግር ኳሱ አሥራ አንድ፣ አሥራ አንድ እየሆናችሁ ነው!” ወዳጄ..ይኸው ስለ እኛ አወራሁ፡፡ “ተልባ በጥባጯ እያለች ጎመን ቀንጣሿ ምች መታት…” የሚለው ተረት “ዘንድሮ አይሠራም…” የሚባልበትን ዘመን ያምጣልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ህብረተሰብ

አንድ ታዋቂ ደራሲ የእርሳሱ ታሪክ በሚል የጻፈው የአጭር አጭር መጣጥፍ እጅግ አስተማሪ ነውና ዛሬ ከትበነዋል፡፡ አንድ ልጅ፤ ሴት አያቱ ደብዳቤ ሲጽፉ አተኩሮ ይመለከታቸዋል፡፡ ብዙ ካያቸው በኋላ፤ “ስለ እኛ ታሪክ ነው የሚጽፉት? ስለኔ ነው?” አለና ጠየቃቸው፡፡ አያትየው፤ ደብዳቤ መጻፋቸውን አቆሙና ለልጅ ልጃቸው እንዲህ አሉት፡- “እርግጥ ነው ልጄ ስለ አንተ ነው የምጽፈው፡፡ ሆኖም ከጻፍኳቸው ቃላት ይልቅ ስለ እርሳሱ ማወቅ ያለብህ ነገር ነው እሚበልጠው፡፡ አንድ ቀን አንተም አድገህ እንደዚህ እንደምገለገልበት እርሳስ እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ” በነገሩ እጅግ ተነክቶ፤ ልጁ እርሳሱን ትኩር ብሎ ተመለከተው፡፡ ሆኖም፤ ከሚያውቀው እርሳስ የተለየ ሆኖ አላገኘውም፡፡ “ይሄ ዱሮም የማውቀው እርሳስ አይደለም እንዴ? ምን የተለየ ተዓምር አለው? ሲል ጠየቃቸው። አያትየውም፤ “አየህ ልጄ፤ እሱ አንተ ነገሮችን የምታይበት ዓይን ጉዳይ ነው፡፡ እርሳስ አምስት ዓይነት ልዩ ጠባያት፤ አሉት፡፡ እነዚህን ልብ ካልክ፣ ምን ጊዜም በዓለም ላይ ሰላም ያለው ልጅ ትሆናለህ፡፡ “የመጀመሪያ ልዩ ጠባዩ፤ ትላልቅ ነገሮችን የመሥራት ክህሎት መኖሩ ነው፤ ሆኖም ምንም ዓይነት ልዩ ክህሎትና ችሎታ ቢኖርህ መንገድህን የሚመራ እጅ መኖሩን አትርሳ፡፡ ያን እጅ አምላክ እንለዋለን፡፡

እሱ ሁልጊዜ እንደ ፈቃዱ የሚመራን ነው፡፡ ሁለተኛው ልዩ ጠባዩ፤ በምጽፍ ጊዜ አሁንም አሁንም መጻፌን አቁሜ ልቀርፀው ይገባኛል፡፡ ያም እርሳሱ ትንሽ እንዲያመው ያደርገዋል፡፡ ሆኖም ከታመመ በኋላ የበለጠ የሰላ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አንተም ህመምህንና ሀዘንህን እየተሸከምክ፣ እየቻልክ መኖርን ከተማርክ የተሻለ ሰው ትሆናለህ፡፡ ሦስተኛው ልዩ ጠባዩ፤ ድንገት የተሳሳተ ነገር ብንፅፍ በላዺስ ተጠቅመን ማጥፋት እንችላለን፡፡ ይሄ የሚያመለክተን አንድ የሠራነው ነገር ስህተት ሆኖ ሲገኝ ማረም መጥፎ አለመሆኑን ነው፡፡ ወደ ትክክሉ፣ ወደፍትሐዊው መንገድ ተቃንተን እንድንጓዝ ይረዳናልና! አራተኛው ልዩ ጠባዩ፤ የእርሳሱ የላይኛው የእንጨት ልባሱ ወይም ቅርፊቱ ሳይሆን ዋናው ከውስጡ ያለው ግራፋይት /እርሳሱ/ ነው ቁም ነገሩ፡፡ ይህ ራስህ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ልብ ማለት እንዳለብህ ትምህርት ይሰጥሃል፡፡ ዋናው የውስጣችን፣ የመሠረታችን ጉዳይ፤ ማለት ነው፡፡ አምስተኛውና የመጨረሻው ልዩ ነገር፤ እርሳስ ባለፈበት ሥፍራ ሁሉ ምልክት ወይም አሻራ ይተዋል፡፡ ልክ እንደ እርሳሱ ራስህን ቆጥረህ ብታስበው፤ እያንዳንዱ በህይወትህ እየሠራህ የምታልፈው ነገር ሁሉ ምልክት ይተዋል፡፡ ስለዚህ ያለፍክ ያገደምክባትን የሕይወት መንገድ ሁሉ አስተውል፡፡

                                                             * * *

ከአያት ከቅድመ አያት የወረስናቸውን ትምህርቶች በአግባቡና በቅጡ ሥራ ላይ ካዋልናቸው ከመሠረታዊ የኑሮ ግልጋሎታቸው ባሻገር አገርን ለማሻሻል የለውጥ አንጓ ይፈጥሩልናል፡፡ የራሳችንን ሰላም የምንፈጥረው ራሳችን ነን፡፡ የሚመራን እጅ/አምላክ እንዳለ ማሰብ ያለብን ራሳችን ነን፡፡ ህይወታችንን ማለትም እራሳችንን በየጊዜው መቅረጽ ይኖርብናል፡፡ ይህንን ስናደርግም የየጊዜውን ህመም ተቋቁመን መሆን አለበት፡፡ ስህተትን አርሞ ወደ ፍትሐዊው መንገድ መጓዝ ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ህይወት ከላይ ከላይ ስትታይ ብልጭልጯ ብዙ ነው፡፡ ብልጭልጯ ግን እንደእርሳሱ የተቀባ የእንጨት ቅርፊት ነው፡፡ ዋናው ውስጧ ነው፡፡ ቡጧ ነው፡፡ ውስጣችንን እናንብብ። አገራችንን እንወቅ፡፡ በውስጥ የሚከናወነውን እናጢን፤ እናውጠንጥን፡፡ ንፁህ ዜጋ በውስጡ የሚካሄደውን ክንዋኔ ሲያውቅ ራሱን ያውቃል፡፡ ቀጣይ መንገዱ ያውቃል፡፡ ለሀገሩ የሚበጀውን ያደርጋል፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ላይ የምንተወውን አሻራ ብናውቅ የአመት የአምስት ዓመቱን፣ የዘለቄታውንም አሻራ እናስተውላለን፡፡ አሻራችንን ጠንቅቀን እንወቅ፡፡ ያም ሆኖ አንዳንዶች የሁሉን ተግባር አልፋና ኦሜጋ ራሳቸውን አድርገው ይፎክራሉ፡፡ “ሁሉ ያማረ በእኔ ነው፡፡ ሁሉን እምሠራ እኔ ነኝ፡፡ ከማንም የተሻልኩ ንፁሕ ነኝ፤ አልተሳሳትኩም፤” በማለት ይፎክራሉ፡፡ ይሄ በተራ ግንዛቤ እንኳ ሲታይ “የሚሠራ ይሳሳታልን” መርሳት ነው፡፡

“ክንፍ አለኝ፣ መልዐክ ነኝ ብለህ አትፎክር ትንኝም ክንፍ አላት፣ ባየር ለመብረር…” ይሉናል ብርሃኑ ድንቄ፡፡ የአደጉና አዳጊ፣ ትላልቅና ትናንሽ አገሮች አንዱ አንዱን የሚያይበት ዐይኑ መለያየቱ እንጂ እንከን አልባ ብሎ አገር የለም፡፡ የዓለም ገዢ ነን የሚሉት ኃያላንም ቢሆኑ፡፡ “ዓለም አቀፍ ዴሞክራቲክ ካፒታሊዝምም ቢሆን እንደዓለም አካላይ ኮሙኒዝም፤ አስተማማኝ ሥርዓት አለመሆኑን ልብ በሉ”፤ ይለናል ጆን ግሬይ፡፡ ዕምነት እምንጥልባቸውን ታላላቅ አገሮች በዲፕሎማሲያዊ ጥንቃቄ እንያዛቸው፡፡ እነሱም ለጥቅማቸው፣ እኛም ለጥቅማችን፤ እንበል። ሲያመሰግኑን “ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ይሏታል”ን “እንዲህ እያልሽ ውቴልሺን ሽጪ” ማለትን እንልመድ፤ ቢያንስ በሆዳችን፡፡ ያለጥቅም እጅ የማይዘረጋበት ዘመን ነው፡፡ በተለይ ዕምነተ ካፒታሊዝማችን ያለዕውቀትና ከልኩ ያለፈ ሲሆን “የባለጌ ሃይማኖት ከጅማት ይጠናል” ነው እሚሆነው፡፡ ፓውሎ ኮሄሎ የተባለ ፀሐፊ፤ “አንዳንድ ታላላቅ መንግሥታት በሽብርተኝነት ላይ የሚካሄድ ጦርነት ባሉት ላይ፣ የዓለም አቀፍ የፖሊስ መንግሥት መፍጠሪያ ዘዴ አድርገው ይጠቀሙበታል” ሲል ይሟገታል፡፡

“እቺ ጠጋ ጠጋ ሣር ፍለጋ ሳትሆን ዱባ ለመስረቅ ነች” እንደሚባለው ነው፤ ማለቱ ነው፡፡ “አንዱ ሲያለማ፣ ሌላው ያደለማ” በሆነበት የአገራችን ሁኔታ ውስጥ፤ ምሥጡን ከመዥገሩ፣ መወቴን ከአለሌ፣ ጨውን ከአሞሌ፣ ቱሪስትን ከፒስኮር፣ ህንዱን ከሳኒያን፣ ዶፉን ከወጨፎ፣ ጐረቤትን ከጐረቤት፣ ኔትዎርክን ከኖ-ወርክ…ለይተን ካልተጓዝን፣ የትም አንደርስም፡፡ እንወቅበት። ዛሬ “ከልጄ ለቅሶ፣ የጌታዬ ደቦ ይበልጣል” የሚል አድርባይ የበዛበት ጊዜ ነው፡፡ ለጥቅም የማይነቀል ባህር ዛፍ የለም፡፡ ባለጊዜን ማወደስ በየሥርዓቱ የሚታይ ክስተት ቢሆንም የከፋ ጊዜ ሲመጣ ባልሠራው የሚሞገስ፣ ባልፀዳበት ንፁህ የሚባል እየበዛ መሄዱ አንድም የአወዳሹን የፈጠጠ ደጅ ጠኒ አዕምሮ፣ አንድም የተወዳሹን ግብዝነት ያሳያል፡፡ ይሄ ደግሞ በምንም መለኪያ አገር ገንቢ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ገና ሥራው ሳይሰራ በመፈክርና ይሄን ላደርግ ይህን ልፈጥር አቅጃለሁ በሚል ከፍ - ከፍ አርጉኝ ማለት፤ “ተዋጊ፤ ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ ሳይሆን፣ ሲመለስ ነው የሚወደሰው” የሚባለውን ተረት መዘንጋት ይሆናል!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

“ሙዚየሙ ያለበት ግቢ በዲሞክራሲ ሂደት ላይ ጉልህ ሚና ተጫውቷል”

ሰዓሊ ግርማ ቡልቲ እና ሰዓሊ ቅድስት ብርሃኔ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም አራት ስዕሎችን በስጦታ አበርክተዋል፡፡ በዕለቱ የሙዚየሙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንደገለፁት፤ ተቋሙ ባለፉት 50 ዓመታት ለባህላዊ ስዕሎች ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ብዙ ሥራዎችን ያሰባሰበ ሲሆን አሁን ደግሞ ዘመናዊ ስዕሎችን ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡ ስለ ሙዚየሙ አመሠራረትና የሥራ ሂደት የሙዚየሙ ኃላፊ ከሆኑት ከዶ/ር ሀሰን ሰኢድ ጋር ቆይታ አድርጌያለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አመሠራረት ታሪክ ምን ይመስላል? ሙዚየሙ እንዲቋቋም የመጀመሪያውን መሠረታዊ ሥራ የሰሩት የፖላንድ ተወላጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ስታንስላቭ ሆይናይስኪ ናቸው፡፡ አይሁዳዊነት ስላላቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደ ካናዳ ሄደው በመማር ላይ ሳሉ ተጋብዘው ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፡፡

ፕሮፌሰሩ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ላይብረሪ እንዲያደራጁ ተጋብዘው በመጡበት ወቅት፤ በ4 ኪሎ ዩኒቨርስቲ ግቢ ያዩዋቸው ተማሪዎች፣ ከተለያዩ ክፍለ ሀገራትና ብሔረሰቦች የተውጣጡ መሆኑ አስገርሟቸው ስለነበር፣ ተማሪዎቹ ባህላቸውን የሚወክል ቁሳቁስ እንዲያመጡ እየጠየቁ ቅርስ ማሰባሰብ ጀመሩ፡፡ በ1955 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ሙዚየም በ6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ ግቢ ሲቋቋም ፕሮፌሰር ስታንስላቭ ሆይናይስኪ ያሰባሰቧቸው ቅርሶች ወደዚህ መጡ፡፡ ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያ ኢትኖሎጂ ሶሳይቲ መስራችም ናቸው፡፡ የሶሳይቲውን ጆርናልም ያዘጋጁ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ሲሆኑ ፕሮፌሰር ስታንስላቭ ሆይናይስኪ ፀሐፊ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ተቋሙ በሁለቱ ሰዎች እየተመራ እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ ዘልቋል፡፡ የተመሠረተበት ዓላማ ምን ነበር? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማጥናት ርዕሰ ጉዳዩ በማድረግ ነው የተነሳው፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ ጥናት ምንድን ነው? ብለው የሚጠይቁ ሰዎች አሉ። የተቋሙ መሥራቾች ሲጀምሩ እንዳመኑበትና ዛሬም ብዙዎቻችን እንደምንስማማበት ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የተለያየ ባሕልና አመለካከት ያላቸው ብሔረሰቦች ተፈቃቅደውና ተከባብረው በአንድነት የሚኖሩበት አገር ናት፡፡ የዚህን ሕዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት … ማጥናት ትልቅ ተግባር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ገናና ስልጣኔ ታይቶ የከሰመባት ምድር ናት፤ ይህ በራሱ ለጥናት ይጋብዛል፡፡

ልክ ሲሪዮሎጂ፣ ኤጀፕቶሎጂ እንደሚባለው የኢትዮጵያም ጥናት ያስፈልጋል በሚል ዓላማ ነው የተቋቋመው፡፡ ሙዚየሙ ምን ስብስቦችን ይዞ ነው ሥራ የጀመረው? የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ከተመሠረተ በኋላ እንቅስቃሴው ሁሉ እንደ ብሔራዊ ሙዚየም ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ስታንስላቭ ሆይናይስኪ የማይሰበስቡት ነገር አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያን ይገልፃሉ የሚባሉ ነገሮችን ሁሉ ከመሰብሰብ ወደ ኋላ አላሉም ነበር፡፡ ቆርኪ፣ የመኪና ታርጋ ሁሉ ይሰበስቡ ነበር፡፡ ቅርስ ማሰባሰቡ በጀመረው መልኩ ነው የቀጠለው? የመጀመሪያው ቅርስ ማሰባሰብ ሥራ በፍላጎትና በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ አሁን አኩዚሽን ፖሊሲ መከተል አስፈልጎናል፡፡ ሙዚየሙ 13 ሺህ የሚደርሱ ታሪካዊ ስብስቦች አሉት፡፡ የተበላሸ ቅርስ መጠገኛ ላቦራቶሪ ግን የለውም፡፡ በፖሊሲ መመራታችን የቅድመ አደጋ ጥንቃቄ ላይ በሚገባ እንድንሰራ ይረዳናል፡፡ ሁሉም ሙዚየሞች የሚመሩበት ፖሊሲ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያትና ዓላማ የሙዚዮሎጂ ኮርስ በዩኒቨርስቲው ግቢ ከ2006 እ.ኤ.አ ጀምሮ ማስተማር ስለጀመርን ትምህርቱን ያገኙ ባለሙያዎች በተለያዩ ሙዚየሞች በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

የሙዚየም ጥናት ኮርሱ ምን ላይ ያተኩራል? የሙዚየምን ሳይንስ ነው የምናስተምረው፡፡ አንድ ሙዚየም ጥራት ያለው ስብስብ እንዲኖረው ከተፈለገ የሚመራበት ፖሊሲ ያስፈልገዋል፡፡ ብሔራዊ የፖስታ ወይም የቡና ሙዚየም አንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነው ትኩረት ያደረጉት፡፡ ሙዚየሞች በማንኛውም አካል ሲቋቋሙ በምን ጉዳይ፣ ለምን ዓላማ … እንደሚቋቋሙ ግልጽ አድርገው እንዲነሱ የሙዚዮሎጂ ትምህርት ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ ሁሉንም አማረን ብሎ ማከማቸት ቅርስ መሰብሰብ ሳይሆን ማበላሸት ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሙዚየም ባለሙያ ጥንታዊ ቅርስ ስላገኘ ብቻ ወደ ሙዚየሙ ማስገባት የለበትም። ለቅርሱ ተገቢ የሆነ ማስቀመጫ አለኝ ወይ? ቅርሱ ቢበላሽ የሚጠገንበት ላቦራቶሪና ባለሙያ ይገኛል? ብሎ ቀድሞ ሳያስብበት ቅርሱን ሙዚየም ቢያስገባ ቅርሱ ተጠብቋል ማለት አይደለም፡፡ የሙዚዮሎጂ ጥናት በቅርስነት ተመዝግበው የተቀመጡትን ቅርሶች በልዩ ጥንቃቄ እንዲያዙ ያግዛል፣ በተቃራኒው ቅርስ ከማግበስበስ እንድንቆጠብም ይረዳናል፡፡

አሰራራችን ሳይንሳዊ ከሆነ የዲስፕሌይ መርህንም እንድንከተል ያስገድደናል፡፡ መርሁ መረጃ የሌለውን ቅርስ ለእይታ አታቅርብ ይላል። ለእይታ ባቀረብከው ነገር ልታስተምር ነውና ቅርሱ የማን እንደነበር፣ ከየት እንደተገኘ፣ ለምን አገልግሎት ይውል እንደነበር፣ መሠረታዊ ምላሾችን ሳታስቀምጥ አታወጣውም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ቅርሱ ለእይታ ቢቀርብ ለአደጋ የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ከሆነና የሥነ ጥበብ ዋጋና ደረጃውም ከተጎዳ ለእይታ እንዲቀርብ አይበረታታም፡፡ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ሙዚየም ቅርሶች ሁሉም መረጃ አላቸው? እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሙዚየሙ የማይሰበስበው ነገር አልነበረም፡፡ ከንጉሳዊያን ቤተሰብ፣ ከቤተክርስቲያናት፣ ትግራይና ጎጃምን ከመሳሰሉ የተለያዩ አካባቢዎች ባህልና ቅርስን የሚያመለክቱ በርካታ ነገሮች ተሰብስበዋል፡፡ ቅርሶቹ ዝርዝር መረጃ ያላቸውም የሌላቸውም ይገኙበታል፡፡ የእኛ ሙዚየም ቤተ መንግሥት ሆኖ ያገለገለ ቤት በመሆኑ የተነሳ ከቤተመንግሥት የመጡ ስብስቦች አሉን፣ ግን ሙሉ መረጃ የሌላቸው ቅርሶችም አሉን፡፡

ይህ አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ ሰሀንን ሰሀን ከማለት ውጭ መቼ ተሰራ? ማን ነበር የሚገለገልበት? ከየት አገር ተሰርቶ መጣ? በግዢ ነው በስጦታ የተገኘው? … ለሚለው ጥያቄ መረጃ የሌላቸው አልባሳት፣ ቦርሳዎች፣ ጫማዎች … አሉ፡፡ የመረጃ እጥረቱን ለመሙላት ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ከላይ እንዳልኩት የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ሙዚየም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ባህልና ቅርስ ፍቅር ባሳደረባቸው ሰዎች ስለነበር፤ ያንን መነሻ በማድረግ ያለ ገደብና ምርጫ ብዙ ነገር ሰብስቧል። የአፄ ኃይለሥላሴና የቤተሰባቸው መገልገያዎች፣ የከፋው ንጉሥ ባህላዊ ዘውድ፣ አርበኞች ተገልግለውበታል የሚባሉ የጦር መሣሪያዎች … የመሳሰሉ በርካታና የተለያዩ ስብስቦች ይገኛሉ። ቅርሶቹ በዚያን ዘመን በዚህ መልኩ ባይሰባሰቡ የመሰረቅና የመጥፋት አደጋ ሊያገኛቸው ይችል ነበር፡፡ ይህ በጥሩ ጎኑ ቢነሳም የቤተመንግሥቱ፣ የሕብረተሰቡ፣ የጦር ሚኒስትሩ፣ የየክፍለ ሀገሩ … ቅርሶች ራሳቸውን በቻሉ ተቋማት አለመሰብሰባቸው የመረጃ እጥረት አስከትሏል፡፡ እንዲህም ሆኖ 13ሺውንም ቅርሶች የመዘገብንበት አክሴሽን ካርድ አለ፡፡ አንድ ሰው ጤና ጣቢያ ሲሄድ እንደሚሰጠው ካርድ እያንዳንዱ ቅርስም የራሱ የሆነ መለያ ቁጥር ያለው ካርድ አለ፡፡ የቅርሱ ሥም፣ የተሰራበት ቦታ፣ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት፣ የተገኘበት አካባቢ፣ ውፍረቱ፣ ቅጥነቱ፣ ክብደቱ፣ የደህንነት ደረጃውና ፎቶውን ጭምር ይዟል፡፡ በካርድ ብቻ ሳይሆን በካታሎግ የተመዘገቡ ቅርሶችም አሉ፡፡ የሙዚየሙ ዋነኛ ተግባርም የቅርሶቹን መረጃ ማሟላት፣ መጠበቅ፣ ማናፈስ፣ ቀጣይ ዕድሜያቸው የሚረዝምበትን አሰራር መከተል፣ ለጥፋትና ስርቆት እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ ማድረግ፣ ለጥናትና ምርምር ምቹ እንዲሆኑ ማመቻቸትና ሥነ ጥበባዊ ዋጋቸውን መጠበቅ ነው፡፡

የሙዚየሙ አደረጃጀት ምን ይመስላል? ሙዚየሙ ያለበት ግቢ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሂደት ላይ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ግቢው ከቤተ መንግሥት ወደ ዩኒቨርስቲ የተለወጠበትንና ዩኒቨርስቲ ከሆነ በኋላ በአገር ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ሂደቶችን በማሳየት ነው የሙዚየሙ አደረጃጀት የተዋቀረው፡፡ በመቀጠል ከልጅነት እስከ ሞት የሚል ክፍል አለ፡፡ በዚህ ውስጥ የልጆች ጨዋታ፣ ትምህርት፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ሞትና ሐውልቶችን ማሳያዎች አሉ፡፡ የንጉሱና የእቴጌይቱ እልፍኝ ሌላው ክፍል ነው፡፡ ለጥናትና ምርምር የሚረዱ በርካታ ስብስቦች ያሉበት ይህ ክፍል፣ ከአፄ ምኒልክ ጊዜ ጀምሮ በአገራችን የታተሙ ቴምብሮች ይገኙበታል፡፡ የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ክፍል ሌላኛው አደረጃጀት ነው፡፡ የክር፣ የትንፋሽ፣ የምት … ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ይገኙበታል፡፡ የሙዚየሙ ሌላኛው አካል አርት ጋለሪው ሲሆን በአብዛኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክን መሠረት ያደረጉ ስዕሎች አሉበት፡፡ የመስቀል ስብስቦች ሌላኛው የሙዚየሙ አካል ነው፡፡

በንጉሡና በእቴጌይቱ መኝታ ክፍል ስላሉት አልባሳት ምን መረጃ አላችሁ? የንጉሥ ኃይለሥላሴና የእቴጌ መነን አልባሳት መሆናቸውን እርግጠኛ የሆንባቸው ስብስቦች አሉን፡፡ ማን ይገለገልባቸው እንደነበረ ባይታወቅም ፊታውራሪ፣ ቀኛዝማች፣ ሊቀመኳስ … መሰል ማዕረግ አመልካች አልባሳትም አሉ፡፡ በአልባሳቱ ላይ የሚታዩት የሙካሽ ሥራ፣ የብረታ ብረት ጌጦችና ፈርጦች ምንነት የተጠኑም ያልተጠኑም ይገኙበታል። በሙካሽ የሚገለጽ የማዕረግ ዓይነት፣ ሙካሽ የት ይሰራ እንደነበር፣ ማቴሪያሉ ከየት እንደሚመጣ፣ የሙካሽ ሥራ ዕውቀት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እንደጀመረ … የመመረቂያ ጽሑፍ ተሰርቶበታል። እኛም ጥናቱን ኮፒ አድርገን የሙዚየማችን አካል አድርገነዋል፡፡ በአልባሳቱ ላይ የሚገኙት የብረታ ብረት ጌጣ ጌጦች “ጋሻ ጉብ ጉብ” የሚባለው ቅርጽ ያላቸውና ከአንድ ወርክ ሾፕ የወጡ መሆኑን አስረግጦ መናገር የሚቻል የጥበብ ሥራ ናቸው፡፡ የት ይሰሩ እንደነበር፣ ከምን ማዕድናት እንደተሰሩ ገና መጠናት ያለበት ነው፡፡ ከአልባሳቱ ቁልፎች ጋር በተያያዘ የተሰራ ምንም ጥናት የለም፡፡ አንጥረኝነትን የምናደንቅበት አቅም ስላልነበረን ዛሬ ላለብን የመረጃ እጥረት አንዱ ምክንያት ሆኗል እንጂ፤ ኢትዮጵያዊያኑ አንጥረኞች “ቡዳ” እየተባሉም ቢሆን ብዙ ነገር መሥራታቸውን የሚያሳዩ በርካታ ቅርሶች አሉ፡፡ ሙዚየሙ የታዋቂ ሰዎችን አልባሳትና የግል መገልገያ ቁሳቁስ እየተቀበለ ማስቀመጡን ቀጥሎበታል፡፡

ይህ አሰራር ሙዚየሞች በተወሰነ ነገር ላይ ትኩረት አድርገው መስራት አለባቸው ከሚለው ጋር አይጋጭም ? አሁን እየሰበሰብን ያለውን ብቻ ሳይሆን 13ሺውንም ስብስቦች በፊት ከሚገኙበት በተሻለ ሁኔታ በየርዕሰ ጉዳዩ ከፋፍለን በመመደብ ለእይታ የማቅረብ እቅድ አለን፡፡ የዩኒቨርስቲው አዲሱ የአስተዳደር ሕንፃ ግንባታው አልቆ ሥራ ሲጀምር፣ በመኮንን አዳራሽ ያሉ በርካታ ክፍሎች ስለሚለቀቁ፣ እነዚህን የሙዚየሙ አካል የማድረግ እቅድ አለ፡፡ በእቅዳችን መሠረት ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም የሕፃናት ክፍል ከነመዝናኛው፣ የአርበኞች ክፍል፣ የደራሲያን ክፍል፣ የባህላዊ ሸክላ ሥራና የአንጥረኞች ክፍል፣ የዘመናዊ ሰዓሊያን ክፍል ይኖሩታል፡፡ ይህንን እቅድና ዓላማ ምክንያት በማድረግም የተለያዩ የአርበኛ፣ የሚሊተሪና ታዋቂ ሰዎች ታሪካዊ ስብስቦችን ከቤተሰቦቻቸው ተቀብለን አስቀምጠናል፡፡

እነዚህ ስብስቦች ሙሉ መረጃ ያላቸው ናቸው። በዚህ መልኩ የታዋቂ ሰዎችን አልባሳት፣ መገልገያ ቁሳቁስ፣ መፃሕፍት ከሰጡን መሐል የፀጋዬ ገ/መድህን፣ የመንግሥቱ ለማ፣ የከበደ ሚካኤል፣ የሀዲስ አለማየሁ፣ የማሞ ውድነህ፣ የጳውሎስ ኞኞ ቤተሰቦች ይገኙበታል፡፡ በመጨረሻ የሚያነሱት ነገር ካለ … ሙዚየሞችን በተመለከተ በአገራችን መስተካከል ያለባቸው ብዙ አሰራሮች አሉ፡፡ አገራችን የሙዚየሞች ዓለም አቀፍ ስምምነትን በ1978 ዓ.ም ፈርማለች፡፡ ስምምነቱ ቅርሶች ወደተገኙበት ምንጭ እንዲመለሱ ያሳስባል፡፡ በውጭ አገራት ያሉ ቅርሶቻችን እንዲመለሱልን የምንጠይቀው በዚህ ምክንያት ነው። ስምምነቱ በአገር ውስጥም ከመገኛቸው ርቀው የሚገኙት ወደ ነበሩበት ይመለሱ ስለሚል በዚህ ዙሪያ ብዙ ሥራ መስራት ያለብን ይመስለኛል፡፡

Published in ጥበብ
Page 5 of 14