የሀዋሳ ጠ/ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የስንብት ደብዳቤ ደረሳቸው

ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም በእስልምና ሀይማኖት በየወህረ የሚከበረውን “ሊቃ” የተሰኘ ሀይማኖታዊ በዓል ለመካፈል ወደ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ሚኬኤሎ ገበሬ ማህበር መልካሜ መሰጊድ የሄዱትና በእነ አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስና አጋሮቻቸው በድንጋይ ተቀጥቅጠው የሞቱት የኢ/ር ጀሚል ገዳዮች በደቡብ ክልል ሀዋሳ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በድጋሚ ተፈረደባቸው፡፡ የሀዋሳ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ታረቀኝ አበራም ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ የስንብት ደብዳቤ እንደደረሳቸው ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ግንቦት 19 ቀን 2004 ዓ.ም በአካባቢው “የሀይማኖት መሪ” እየተባለ የሚጠራው አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ ነገ ከአዲስ አበባ የሚመጡና የሊቃ በዓላችንን ሊያበላሹ የተዘጋጁ ሰዎች አሉ ሲመጡ በዱላ ደብድባችሁ ደሉ በሚል ባስተላለፈው ትዕዛዝ ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም በበዓሉ ላይ የተገኙት ኢ/ር ጀሚል ሀሰን በድብደባው ህይወታቸው ሲያልፍ በበርካቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የቡታጅራ እና አካባቢው ከፍተኛ ፍ/ቤት ህዳር 7 ቀን 2005 ዓ.ም የግድያው ዋና መሪ፣ አዘጋጅና አዛዥ እንዲሁም የግድያው ቀድሞ ጀማሪዎች ናቸው በተባሉት በአቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ፣ በወንድማቸው ነሲቡ ሰይድ ፋሪስ፣ በወልዩ ቦንሱሞ እና በሁሴን አብደላ ላይ በሶስት ተደራራቢ ወንጀሎች መስርቶ በግድያው ጠንሳሽና በወንድሙ ላይ የ14 እና የ19 ዓመት ፍርድ ያሳለፈ ሲሆን በሌሎች 20 ተባባሪዎች ላይ እንደየጥፋታቸው መጠን ከስምንት እስከ 11 ዓመት ፈርዶባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በውሳኔው ቅር የተሰኘው የቡታጅራ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ለደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሆሳዕና ምድብ ችሎት ይግባኝ ሲል ወንጀለኞቹ በበኩላቸው ሀዋሳ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ብለው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በጠ/ፍ/ቤቱ ፕሬዚዳንት በአቶ ታረቀኝ አበራ የተመራው ችሎት የወንጀለኞቹን ይግባኝ በደንብ መርምሮ ካየ በኋላ የአቃቤ ህግን ይግባኝ መዝገብ ከሆሳዕና በማስመጣትና በማጣመር ወንጀለኞቹን በተለይም የግድያውን ሂደት ጠንስሰዋል፣ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ባላቸው ወንድማማቾች አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ እና በነሲቡ ሰይድ ሰልማን ላይ የ14 እና የ19 ዓመት ፍርዳቸውን አቃቤ ህግ የቅጣት ማክበጃ አላቀረበም በሚል ወደ አምስት እና ወደ ዘጠኝ አመት ዝቅ ያደረገ ሲሆን የግድያው ተባባሪ ናቸው ያላቸውን ቀሪዎቹን ፍርድ ወደ አንድ አመት ከስምንት ወር ዝቅ በማድረግ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በእስር ቤት የቆዩበትን በማስላት በነፃ ያሰናበታቸው መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚህ ውሳኔ እንባ ሲያፈሱ የነበሩት የሟች ቤተሰቦችና አቃቤ ህግ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳይ እንዲታይ ይግባኝ ያሉ ሲሆን የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለወራት ያህል ከመረመረ በኋላ በነፃ የተለቀቁት ወንጀለኞች ሊለቀቁ አይገባም በሚል በሬዲዮና በጋዜጣ ያስጠራ ሲሆን ወንጀለኖቹ በመሰወራቸው ሊቀርቡ እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡ ይህን ጉዳይ በጥልቀት ሲመረምር የቆየው የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አምስት ዳኞችን ከሰየመ በኋላ ባለፈው ማክሰኞ ባዋለው ችሎት ፍርድ ሰጥቷል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ የቀለለውን ቅጣት በቡታጅራ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍርድ የበለጠ በሆነ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

የግድያ ወንጀሉን ጠንስሰዋል መርተዋል ባላቸው አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሽ ወንድማማቾች በአቶ ስልማን ሰይድ ፋሪስ ላይ የ18 ዓመት እስራት ሲፈርድ ግድያውን በማስጀመርና በጭካኔና ነውረኝነት በተሞላበት ሁኔታ ኢ/ር ጀሚልን ከደበደበ በኋላ በላያቸው ላይ ትልቅ ድንጋይ ጭኖባቸው ሄዷል ባለው በአቶ ነሲቡ ሰይድ ፋሪስ ላይ የ19 አመት ከ6 ወር እስራት መፍረዱ ታውቋል፡፡ ቀሪዎቹ የተሰዎሩት ሰዎች እና የግድያው ተባባሪ ናቸው ሆን ብለው ንብረት አውድመዋል በተባሉት 14 ሰዎች ላይ በሌሉበት የ16 ዓመት እስራት ፈርዶባቸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢንጂነር ጀሚልን ግድያ የይግባኝ ጉዳይ በደቡብ ክልል ጠ/ፍር ደቤት ሲመሩ የነበሩትና የወንጀለኞቹን የ14 እና የ19 አመት ቅጣትና የ11 አመት ቅጣት ወደ አምስት አመት እና ወደ ዘጠኝ አመት የቀሪዎቹን ደግሞ ወደ አንድ አመት ከስምንት ወር በማቅለል እንዲለቀቁ ያደረጉት እንዲሁም የደቡብ ክልል ቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ታረቀኝ አበራ ትምህርት እንዲማር በሚል ሰበብ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የስንብት ደብዳቤ እንደደረሳቸው የአዲስ አድማስ ምንጮች ገልፀዋል፡፡

የቡታ ጅራ ማረሚያ ተቋም ሃላፊ ኮሚንደር ወንድወሰን አበባም ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን እነዚሁ ምንጮች ገልፀውልናል፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 2006 በወጣው እትማችን ላይ የኢንጂነር ጀሚልን የግድያ ሁኔታ የፍርድ ቤት ሂደትና የቡታጅራና አካባቢው ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔን፣ የይግባኙን ሂደትና ውሳኔዎችን በተለከተ ሃዋሳ በመሄድ የጠቅላይ ፍ/ቤቱን ፕሬዚዳንት አቶ ታረቀኝ አበራን፣ የሃዋሳ ፍትህ ቢሮ ሃላፊዎችን የቡታጅራ ማረሚያ ተቋም ሃላፊ ኮማንደር ወንደሰን አበበን፣ የቡታጅራና አካባቢው ነዋሪዎችን እንዲሁም የሟች ቤተሰቦችን አናግረን ሰፊ ዘገባ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ስራ አስኪያጅና ሌሎች ከፍተኛ ሃላፊዎች፤ ዶዘር ለማስጠገን የወጣውን ጨረታ ያለ አግባብ ለአንድ ድርጅት በመስጠት በሙስና የተከሰሱ ሲሆን ፍ/ቤቱ፤ የተከሳሾችን መቃወሚያና የአቃቤ ህግን መልስ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 16 ቀጠሮ ሠጥቷል፡፡
ዶዘር ለማስጠገን በወጣ ጨረታ በመንግስት ላይ ከ224ሺ ብር በላይ ጉዳት አድርሠዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ብዙነህ አሠፋ፣ የንግድ ክፍል ዋና ሃላፊው አቶ አበባዬህ ታፈሠ፣ የግዥ ቡድን መሪው አቶ መስፍን ደምሠው፣ የመስክ መሣሪያ ጥገና አገልግሎት ሃላፊው አቶ አብደላ መሃመድ፣ የጠቅላላ ሂሣብ ቡድን መሪው አቶ በለጠ ዘለለው፣ የማቴሪያል ፕላኒንግና ኢንቨንትሪ ማናጅመንት ቡድን መሪው አቶ ታደሠ ኃ/ጊዮርጊስና  የእቃ ግዥ ባለሙያው አቶ ሣሣሁ ጌታቸው ናቸው፡፡  
የእቃ ግዢው ባለሙያ አቶ ሳሳሁ ጌታቸው፤ “ኮማትሱ 801 ዶዘር” የተሠኘውን ተሽከርካሪ ለማስጠገን ለወጣው ጨረታ ከተለያዩ ድርጅቶች ዋጋ መሠብሠብ ሲገባቸው “አንድ አቅራቢ ብቻ ነው ያለው” በማለት ቲኖስ ኃላ.የተ.የግ.ማ ከተባለው ድርጅት ብቻ ዋጋ  ያቀረቡ ሲሆን የቀሩት የስራ ሃላፊዎች ደግሞ ሶስት እና ከዚያ በላይ ተጫራቾች መሳተፍ እንደሚገባቸው እያወቁ አንድ ብቻ ተጫራች የተሣተፈበትን፣ ተጫራቹም የንግድ ፈቃድ ማቅረቡንና ግብር መክፈሉን ሣያረጋግጡ እንዲሁም አማራጭ የእቃዎች ዋጋ ሣያዩ ግዢው እንዲከናወን በማድረግ በመንግስት ላይ ከ224ሺ ብር በላይ ጉዳት አድርሠዋል  ተብሏል፡፡
አቃቤ ህግ ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሠው እና የሠነድ ማስረጃውን አያይዞ ያቀረበ ሲሆን ተከሣሾቹ ከትናንት በስቲያ ለዋለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት  የክስ መቃወሚያቸውን በጠበቃቸው በኩል አቅርበዋል፡፡ በእለቱ የተከሣሾች ጠበቃ፤ “ከተከሳሾቹ መካከል የጨረታ ኮሚቴ አባል ያልሆኑ ስላሉ ተለያይቶ ይቅረብልን፣ ለክሡ መነሻ የሆነው ዶዘር ለጥገና የገባው በመድህን በኩል ነው፣ የስኳር ድርጅት የግዥ መመሪያ ለመድህን የግዥ መመሪያ አይሆንም” በማለት መቃወሚያቸውን አቅርበው ክሡ እንዲነሣላቸው ጠይቀዋል፡፡ የጨረታ ኮሚቴውን በተመለከተ የተነሣው ጉዳይ ምስክሮቼንና የሰነድ ማስረጃ በማቀርብበት ጊዜ ሊነሳ የሚችል ነው፣ ያለው አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ዶዘሩ የፋብሪካው መሆኑን አመልክቶ፣ ከመድህን ጋር ተያይዞ የቀረበው አግባብ አይደለም፤ በማለት ተከሳሾች ክሱ እንዲነሳ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ይደረግልኝ ሲል ጠይቋል፡፡ ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 16 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Published in ዜና

በአሚር ዩኒስ ረሐስ የተፃፈው “የምሥራቅ ፈርጦች” የተሰኘ ታላላቅ የሐረሪ ተወላጆችን ታሪክ የያዘ መፅሃፍ ባለፈው ሳምንት ለንባብ በቅቷል፡፡ ስምንት የሚደርሱ የሐረሪ ሊቃውንቶችና የታሪክ ምሁራንን የሚያስተዋውቀው መፅሃፉ፤ መታሰቢያነቱን የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ ለነበሩት ለአብዱል ሐፊዝ ከሊፋ መሐመድ እና ለመሐመድ ኢብራሒም ሱሌይማን አድርጓል፡፡
በመጽሐፉ ታሪካቸው ከተካተቱት መካከል የሳይንስ ሊቁ ፕሮፌሰር ዘኪ አብዱላሒ፣ የታሪክ ምሁሩ አህመድ ዘካሪያ፣ የሐረር የነፃነት አባት በሚል የተገለፁት ሼህ ኢብራሂም ጋቱርና ሌሎች ለሐረሪ ህዝብና ለኢትዮጵያ እድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦች ይገኙበታል፡፡ ግለሰቦችም ትውልድ ሊማርበት የሚችል  አኩሪ ታሪክ አላቸው የሚለው ደራሲው፤ በመፅሃፉ ታላላቅ ሥራዎችን የሰሩና የታሪክ ባለውለታ የሆኑ የጥቂት ሐረሪዎችን ታሪክ ለመዳሰስ መሞከሩን በመግቢያው ላይ ገልጿል፡፡ በ413 ገፆች የተቀነበበው መፅሃፉ፤ በ80 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩል በገጣሚ አለማየሁ ነጋ የተፃፉ ግጥሞችን ያካተተ ‹‹የተመዘዙ ሰበዞች›› የተሰኘ የግጥም መድበል ታትሞ ባለፈው ሳምንት  ለገበያ ቀርቧል፡፡ በ72 ገፆች ሰባ ሁለት ግጥሞችን የያዘው የግጥም መፅሐፍ በ30 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

Page 14 of 14