በማርቭል ስቱዲዮ የተሰራው “ዘ አቬንጀርስ” 220 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ፊልሙን ዲያሬክት ያደረገው ጄስ ዌይደን ነው፡፡ በፊልሙ ላይ ቡድን ከመሰረቱት ታዋቂ ጀብደኛ ገፀባህርያት መካከል በቀዳሚነት የ”ካፒቴን አሜሪካ” ፊልም ተዋናይ ክሪስ ኢቫንስ፤ የ”አይረንማን” ሮበርት ዳውኒንግ ጁኒዬር፤ የ”ቶር” ክሪስ ሄስሞስ፤ የ”ሃልክ” ማርክ ሩፋሎ፤ የ”ሃውካይ” ዠረሚ ራነር እንዲሁም የ “ዘ ብላክ ዊዶው” ስካርሌት ጆሃንሰን ተሳትፈዋል፡፡ በተጨማሪም ሳሙኤል ጃክሰን፣ ጅዌኔትዝ ፓልትሮው እና ቶም ሂድልስተንም በፊልሙ ላይ የሰሩ ሌሎች ዝነኛ ተዋናዮች ናቸው፡፡ማርቭል ስቱዲዮስ “ዘ አቬንጀርስ”ን ለመስራት ስድስት አመት የፈጀበት ሲሆን ከዚህ ቀደም ኩባንያው የሰራቸውን የሱፐር ሂሮ ፊልሞች በማዋሃድ በ”ዘ አቬንጀርስ” ያስመዘገበው ስኬት ተከታታይ ፊልሞችን ለመስራት አነሳስቶታል ተብሏል፡፡ ማርቭል ስቱዲዮ በሚያሳትማቸው የኮሚክ መፅሃፍት ላይ የተሰሩትና የ”አቬንጀርስ”ን ስድስት ዋና ዋና ገፀባህርያት የሚተውኑት ጀብደኞች በተናጠል በተሰሩባቸው ፊልሞች በዓለም ዙርያ ከ2.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገብተዋል፡፡ እነዚህ ጀብደኛ ገፀባህርያትን በቡድን የያዘ ራሱን የቻለ ኮሚክ መፅሃፍ በስቱዲዮው የተዘጋጀ ሲሆን “ዘ አቬንጀርስ” በሚል በመጀመርያ ክፍል የተሰራው ፊልም ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በኮሚክ መፅሃፍት ላይ የተሰሩ ፊልሞች የ2012 አጋማሽ ገበያን ይቆጣጠራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይ በ”ዘ አቬንጀርስ” እና በ”ዘ ዳርክ ናይት ራይዝስ” መካከል ከፍተኛ ፉክክር እንደሚፈጠር ተገምቷል፡፡ “ቦክስ ኦፊስ ባይ ነምበርስ” በድረገፁ እንዳመለከተው፤ በኮሚክ መፅሃፍት ውስጥ ያሉ ገፀባህርያትን በመጠቀም የተሰሩ ፊልሞች ከ5 ቢ. 345 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝተዋል፡፡