Saturday, 04 May 2024 10:59

ሁሉ ይከበራል፤ ግና ሁሉ ይታመናል?

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ
Rate this item
(2 votes)

በተፈጥሮዬ ከሽማግሌዎች (ከታላላቆች) ጋር ማውራት በጣም ደስ ይለኛል። ሽማግሌዎችን በጣምም አምናለሁ። የሚያወሩኝ፣ የሚነግሩኝ ሁሉ እውነት ይመስለኛል። በርግጥ ይህ ሁልጊዜ እውነት ሊሆን እንደማይችል አይጠፋኝም። ግና ምን አደርጋለሁ፤ በቃ ትልልቅ ሰዎችን አምናለሁ።
፩. ሽማግሌው ፈረንጅ
መልኩን አይቶ ብቻ ይረባል አይረባም
ክፉ ነው ደግ ነው ማለት አይገባም …
በሰው አገር በእንግድነት እያለን፣ ከእለታት አንድ እለት፤ የታዋቂውን የሃገሬን ድንቅ የሙዚቃ ባለሙያ፣ የዋሊያስ ባንዱን ኪቦርዲስት ሀይሉ መርጊያን ‹ሰሜንና ደቡብ› የተሠኘውን (የመሣሪያ ቅንብር) እየሠማሁና ማልቀስ እያማረኝ፣ ከፈረንጅ አገር ፓርክ ውስጥ ተቀምጬ እተክዛለሁ:: ይገርማልኮ መቶ ሺዎች በመድረክ ያጨበጨቡለት ይህ ድንቅ ሙዚቀኛ፣ ከሃገሩ ተሰዶ በዋሺንግተን በታክሲ ሹፌርነት ያገለግላል ባሉኝ ጊዜ እምባዬ መጥቶብኝ ነበር።
ከፓርኩ ፊት ለፊት ከመግቢያው ከተንበሪ አካባቢ ከሚገኘው የለስላሳ መጠጦች ማደያ ማሽን ዶላሬን አጉርሼ ያወጣኋትን የጣሳ መጠጥ እየተጎነጨሁ፣ በእጄ የቀረኝን ዝርዝርና ድፍን ዶላር እቆጥራለሁ:: ባለ አንድ፣ ባለ አስር፣ ባለ ሃያ፣ ባለ ሃምሳ ምናምን .... ። እንዴት እንደሆነ ባላውቅም የገንዘብ ኖቶች አዲስ ሲሆኑ የሆነ የሚፈጥረው አዲስ የግርታና በቶሎ ያለመልመድ መንፈስ አለ። ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም አገር ቤት ባንክ ተቀጥሬ መስኮት ላይ ገንዘብ እየቆጠርኩ ተቀባይና አዳይ ሆኜ የሰራሁ ቢሆንም።
በድንገት አንድ ሁለቴ በአካባቢዬ እንደ አሞራ ይዞረኝ የነበረ ቀጭን ሽማግሌ፣ ነጭ የአገሬው ሰው፣ ወደ እኔ ቀረብ ብሎ በእንግሊዝኛ ያናግረኛል። ከጆሮዬ የዶልሁትን ማዳመጫ ወጣ አድርጌ፤
 “ይቅርታ የተናገሩኝን አልሰማሁትም ጌታው!” አልሁት (በቋንቋው)።
“What a wonderful day sir! I think you are listening to a jazz instrumental music, of the likes Desafinado or Ray Charles or Oscar Peterson.... “ ሽማግሌው ከአነጋገሩና ከመልኩ ሜክሲካን ይመስላል።
በመጀመሪያ ግርታ ወረረኝ። በምን አወቀ ብዬ ነው። ለጥቄ ደሞ የዘረዘራቸውን ስሞች ዘፈን እየሠማሁ አልነበረም፣ ግን ያው ኢንስትሩመንታል ነበር። እውነትም ልብ ብዬ ወደ ራሴ ሳጤን፣ የማዳምጠው ሙዚቃ ድምፅ በጣም ከፍ ብሎ ኖሮ ከማዳመጫው አልፎ በጆሮ ማዳመጫው ትንሽዬ ስፒከር ሲንጫጫ ወደ ውጭ ይሰማ ነበር።
የውጭ ሃገር ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ከእኛ የሚሻሉት እንግዳ ሰዎችን እንዴት ማናገር እንዳለባቸው ጠንቅቀው በማወቃቸው ነው። አንዴ ስለ ቀኑ ማማር፣ ሌላ ጊዜ ስለ በረዶው፣ ደሞ ሌላ ጊዜ ስለ ቀስተደመናው ውበት በማውራት ንግግር በድንገት ሊያስጀምሩ ይችላሉ።
ሽማግሌውን ሳየው ኑሮ የተመቸው አይነት አይመስልም። ተጎሳቁሏል። ፈገግ ብሎ እያወራኝ ሞባይሉን ይደነቋቁላል። ህይወት ለማንስ ሞልቶ ያውቃል? ብዬ በማሰብ ስለሠውየው ያለኝን ግምገማ አቆምኩ። መፅሐፍን በሽፋኑ አትገምግሙ ይባላል አይደል?! ፈገግ ብዬ እየሠማሁ ያለሁት የማንን ድንቅ ጨዋታ እንደሆነ በደስታ ደህና አድርጌ አብራራሁ። በመቀጠል ‹አቢቹ ...› እና ‹ሼመንደፈር› የተሰኙትን ቅንብሮች ድምፁን ከፍ አድርጌ ለእንግዳው ሰው አሰማሁት። ሰውየው አይኖቹን ጨፍኖ እየተወዛወዘ አዳመጣቸው። አይኖቹን ሲገልጥ ያቀረረ እንባ በፀሀይዋ ብርሃን ሲንፀባረቅ ብሌኖቹ ላይ ያየሁ መሰለኝ። (መሠለኝ ነው!)
“በእውነት ድንቅ ቅንብሮች ናቸው። ስላስደመጡኝ በጣም አመሠግናለሁ። አሁን የሙዚቃዎቹን ባለቤት ስላወቅሁ ከኔ ስልክ ላይ አዋድደዋለሁ። መልካም ቀን ይሁንልዎ።” አለና ጉዞውን ለጠቀ።
በቃ ይህንን ሊያናግረኝ ነበር የመጣውና ወሬ ያስጀመረኝ ማለት ነው? ብዬ ተገረምኩ። የስልኬን ድምፅ ቀነስ አድርጌ ማዳመጫዬን ወደ ጆሮዬ ለማድረግ ስዘጋጅ ሰውየው መለስ አለና፤ “በነገራችን ላይ እስኪ እነዚህን ዝርዝር ብሮች (ዶላሮች) ድፍን ያድርጉልኝ? “ አለኝ፤ በጨዋ ደንብ የባለ አስር ኖቶቹን እየሠጠኝ።
“ችግር የለውም “ አልኩ እየተቀበልኩት። አራት ባለ አስር ነበሩ።
“አራት ብቻ ናቸው’ኮ።” አልኩ ደጋግሜ እየቆጠርኩ።
“ኦው ይቅርታ ...” አለና አንድ ባለ አስር ኖት ከኪሱ አውጥቶ ጨመረልኝ። ባለ ሃምሳ ድፍን አቀበልኩት።
አመስግኖ ተቀብሎ ኖቱን እያስተዋለ፤ “አዩ ጌታው እኔ ሆምለስ ነኝ። ስለዚህ ዝርዝር ኖቶች ከኪሴ ሲበዙ ለአያያዝ አያመቹኝም፤ እንዲያውም ችግር ይጠሩብኛል ብዬ ነው።” አለኝ እየሳቀ።
“ገባኝ …” አልኩ።
የሃምሳ ብር ኖቱን በድጋሚ በእጄ ከያዝኩት የቅድሙ ባለ አስር ዝርዝሮች ላይ እያኖረ “ታዲያ ይሄንን ልጨምርልዎትና አንድ ላይ ድፍን መቶ ያድርጉልኛ ካለዎ?”
አሰብ አድርጌ አንድ ላይ ቆጠርኩት፤ አንድ መቶ። “ይቻላል ... “ አልኩና ድፍን ባለ መቶ አስጨበጥኩት።
ሰውየውም ሰርከስ እንደሚያሣይ ሰው አንድ እጁን ወደ ጀርባው ቆልፎ፣ “ይባረኩልኝ ጌታው!” ብሎ እጅ ነሳና በፍጥነት ፓርኩን አቋርጦ ከአይኔ ጠፋ።
እንደተለመደው ማዳመጫዬን ወደ ጆሮዬ ደንጉሬ ጥቂት የሙዚቃ ዘለላዎችን ካጣጣምኩ በኋላ ነበር በእጄ የያዝኩትን ገንዘብ ለመቶኛ ጊዜ በቆጠራ የደጋገምኩት። ሽማግሌው ሰርቶልኝ ኖሯል። እንደምን አድርጎ ሃምሳዋን እንደወሰደብኝ ተገለጠልኝና ራሴን እያወዛወዝኩ ሣልፈልግ ፈገግ ብዬ ቆምኩ። ሞጭላፋ ኖሯል። እስከ መግቢያው ድረስ ሮጥ ሮጥ አልኩ። ግራና ቀኝ ባስተውልም ምንም የለም። በድጋሚ ፈገግ አልኩ።
እንዲያው ለመሆኑ ስለ ሙዚቃስ ያውቅ ኖሯል? ብዬ ራሴን ጠየቅሁ። አሁንም ዘግይቶ ሀሳቡ በራልኝ። ወደ ጎግል ሠሌዳ ሄጄ ቶፕ የሆኑ የጃዝ ኢንስትሩመንታል ሙዚቃዎች ብዬ ስጠይቅ የቅድሞቹ ሠዎች ስም ተዘረገፈልኝ::
Desafinado – Stan Getz & Charlie Byrd.
One Mint Julep – Ray Charles.
Afrikaan Beat – Bert Kaempfert & His Orchestra.
Night Train – Oscar Peterson Trio...... ወዘተ ...
አሁን በደምብ ሳቅሁ:: አዲዎስ። አዲስ እውቀት ግን አገኘን። ‹ሽማግሌዎች ሁሉ ሊከበሩ ይገባል፣ ሁሉም በጅምላ ግን አይታመኑም›። እናም እንዲህ የሚል የከበደ ሚካኤል /የክቡር ዶክተር/ ቅኔ ወደ ሃሳቤ መጣ።
የመልኩ ደም ግባት ይመር አይመር
ሰው ጠባዩ ታውቆ ፊት ሳይመረመር
መልኩን አይቶ ብቻ ይረባል አይረባም
ክፉ ነው ደግ ነው ማለት አይገባም።
፪. የጋቸኔው አባወራ
ምን ያደርግልኛል ከረባት አሳሪ
ይምጣ የወሎ ልጅ ባውንድ ዘርዛሪ
በፊት ግዜ። ከእለታት ሌላ እለት፤ እዚሁ አዲስ አበባ ወደ ዘነበወርቅ ሆስፒታል ታክሲ ውስጥ እያለሁ ከጎኔ የነበሩትን አዛውንት ከቀልቤ ሆኜ አላየኋቸውም ነበር። ሰዓት ሲጠይቁኝ ነበር ልብ ያልኳቸው። ሽርጥ አገልድመዋል። ከአናታቸው ላይ ጣል ያደረጓት ቆብም አርጅታለች። ሰዓት ከነገርኳቸው በኋላ ተዋወቅን።
“ወዴት እየሄዱ ነው? “
“ዘነበወርቅ ቀጠሮ አለኝ። እግሬ ቆዳ ላይ የሚያሳክክ ነገር ወጥቶብኝ እንደቀልድ ቅጠላቅጠል ስቀባ ከርሜ፣ ደብረብርሃን ሆስፒታል ብሔድ ወደዚህ ሪፈር አለኝ። አሁን እንኳ መድሃኒቱን እየቀባሁ እየተሻለኝ ነው። ይመስገን።”
“የትውልድ መንደርዎ የት ነው?”
“ልዩ ስሙ ጋቸኔ ይባላል። ከአንኮበር አልዩአምባ ከደረስክ በኋላ በእግር፤ አንዳንዴም በተገኘው ትራንስፖርት ነው የሚኬደው።”
እንዲህ እንዲህ እየተጨዋወትን ከደረስን በኋላም አልተለያየንም። አብረን ዋልንና ወዳጅ ሆንን። ማታ ማታ የሚያድሩት ሆቴል እንደሆነና አሁን ግን ገንዘብ እየጨረሱ ስለሆነ ህክምናው ሳይጠናቀቅ ሊመለሱ መሆኑን ሲነግሩኝ፣ የተወሰነ ቀን እንግዳ ሆነው እኔ ቤት ማደር እንደሚችሉ አግባባኋቸውና እንግዳዬ ሆኑ። ሃጂ የሱፍ ወዳጄ የሆኑት በዚህ ምክንያት ነበር። ከዚያ ህክምናቸውን ጨርሰው ከሄዱ በኋላ በሳምንት ቢበዛ በአስራ አምስት ቀን እየደወሉ ይጠይቁኛል። አንዳንዴ ማር ይልኩልኛል። ልጄ ይሉኛል።
ባለፈው ዓመት ልጃቸውን /ረውዳን/ ስለሚድሩ /ኒካህ ስለምታስር/ ተጠራሁና ወደዚያው ለመሄድ ተስማማሁ። በዚያውም አገር ጉብኝት ነውና ደስ ብሎኝ ነበር።
ቀኑ ሲደርስ በመጀመሪያው ቀን ደብረብርሃን ሄጄ አደርኩ፤ በማግስቱ ማልጄ ተነስቼ ወደ አንኮበር ከተማ ገሰገስኩ። መዳረሻዬ ወደሆነችው፣ ከአንኮበር ትንሽ ዝቅ ብላ ወደምትገኘው አልዪ አምባ ከተማ ሲረፋፍድ ደረስኩ። ከዚያ ከከተማው ሃጂ በቅሎ ይዘው ይጠብቁኝ ነበር። የሚቀጥለው ጉዞ ራቅ ያለ ስለሆነ ነበር አዛውንቱ በቅሎ ይዘው የሚጠብቁኝ። ቁርስ ከከተማዋ ከቀማመስን በኋላ ጉዟችንን ተያያዝነው። ሞቃት ነበር። እኔ በበቅሎ ተቀምጬ ሃጂ ከፊት እየሳቡና አህያ እየነዱ። ከሃምሳ አመት በላይ የዕድሜ ልዩነት ቢኖረንም ከበቅሎ ላይ የተቀመጥኩት እኔ ነበርኩ። በሻንጣዬ ለቆይታዬ ይረዳኛል ብዬ ያሰብኩትን ተጠቅልሎ የመተኛ ሻንጣ /ስሊፒንግ ባግ/፣ መቀየሪያ ልብሶች፣ ለስጦታ የሚሆኑ ሽቶዎችና አንዳንድ ነገሮች አጭቄ ስለነበር በአንዲት ኮሳሳ አህያ ጭነናል። አህያዋ እያንዛረጠች ከፊት ከፊት ዘክዘክ ትላለች።
ሽማግሌው በጣም ጠንካራና ጨዋታ አዋቂ ናቸው። ጥርስ አያሥከድኑም። አስራ ሁለት ልጆች ከስድስት ሴቶች አሏቸው። እያገቡ ይፈቱ ነበር። እድሜያቸው ወደ ሰማንያዎቹ ግማሽ አካባቢ ይመስላል። በትክክል አያውቁትም። አሁን በመጨረሻ የሚኖሩት ከወጣቷ እና ሁለት ልጆች ከወለደችላቸው፤ በሃያዎቹ መጨረሻ አካባቢ ከምትገኘው ባለቤታቸው ኑሪያ ጋር ነው። ሌሎቹ ልጆቻቸው በሙሉ ግን ያገቡና የወለዱ ናቸው። አንዳንዶቹም ሃጂ የሡፍ አባታቸው እንደሆኑ አያውቁም።
“ለምን አያውቁም?” አልኳቸው እየተጓዝን።
“ድሮ ወደል ጎረምሳ ሳለሁ አጥፊ ነበርኩ። ሙስሊም እባላለሁ’ንጂ ስለ ሃይማኖቱም ብዙም አላውቅም ነበር። ልጅ መውለድም አልፈልግም ነበር። የምኖረው አፋር ነበር። የመጀመሪያ ሚስቴን ያገባሁት እዚያ ነው። ስታረግዝ ጥያት ጠፋሁ። ከወለድኩ ድሃ የምሆን ይመስለኛል። ከዚያ ከእርሻ ወደ ንግድ ገባሁ። ከደሴ አዲስ አበባ እነግዳለሁ። ገንዘብ አገኛለሁ፤ ቁማር እጫወታለሁ፣ እጨፍራለሁ። ሁለተኛውን ልጄን የወለድኩት ከቡና ቤት ሴት ነበር።”
“ደሞ በዚያን ጊዜ ምን ቁማር ይጫወታሉ። ቁማር ነበር’ንዴ?”
“አይ ፈዛዜ፤ ካርታ የተጀመረው በአንተ ዘመን ብቻ ነው የሚመስልህ! በወጣትነታችን ያላየነው የለም ስልህ! …”
ፀሀይ ከአናታችን ትክክል በመሆኗ ላቤ በጀርባዬ ይንቆረቆራል። ሽማግሌው ከበቅሎዋ ፊት ፊት ሲራመዱ ሰማንያ አመት የኖሩ አይመስሉም። ሽርጤን አንስቼ በላብ ከተነከረው አናቴ ላይ ጠመጠምኩት።
ዘወር ብለው አዩኝና፤ “ከፈፋው አካባቢ ስንደርስ ግራር አለች። ከዚያ ጥቂት አረፍ ብለን ፀሀይዋን እናሳልፋለን። አይዞህ! በርታ! “ አሉኝ።
ላቤን እየጠራረግሁ “እሺ! “ አልኩ።
ቅድም በዚህ ሠዓት ጉዞ አንጀምርም ሲሉኝ ግዴለም እችለዋለሁ ብዬ በመውጣቴ ተፀፅቻለሁ። ሰማዩ ላይ ለላንቲካ እንኳ የሚታይ የደመና ዘር የለም። ፀሃይ የመጨረሻ ሃይሏን የምታሳየው በዚህ ምድር ይመስላል። ከበቅሎዋ ጀርባ ላይ ተቀምጬ በስልቻ እንደታሰረ ማር ወዲያ ወዲህ እዋትታለሁ። እጅግ ደክሞኛል።
“ወርጄ በእግሬ ልሞክረው ይሆን ሃጂ!” አልኩ ለምክር ብጤ።
“ኸረግኝ! አትችለውም ልጄ! ረጅም መንገድ ስለሆነ በበቅሎዋ ጥቂት ሞክር ! … “
“ይሁን ግዴለም ብድሬን እመልሳለሁ። ወደፊት በደንብ እጦርዎታለሁ። አደከምኩዎ! “
ነጫጭ ጥርሶቻቸውን በረጅሙ የጥርስ መፋቂያቸው እየቦረሹና ምራቃቸውን እንጢቅ እያሉ በፈገግታ፤ “መጦሩንማ ይኸው ከበቅሎ ላይ ተቀምጠህ ጀምረኸዋል! …” ሸረደዱኝና ሳቃቸውን በረጅሙ አሰሙ። እኔም ሳቄን መቆጣጠር አልቻልኩም።
“አይዞህ ስቀልድብህ ነው። ለኔ እንደልጅ ሆነህ የታዘዝከኝና ከዚያ ከቤትህ የተንከባከብከኝ፤ ዛሬ ደግሞ እሺ ብለህ መምጣትህ በራሱ ሽልማቴ ነው። ተባረክ ልጄ። አላህ ይባርክህ።”
“አሜን! … እኔምልዎት ሃጂ፣ ደሴ አዝማሪ ቤት የተደረገውን ከእንደገና ያጫውቱኝ እስኪ “ አልኩ ጨዋታ እንዲቀጥሉልኝ።
ረጅም ዘንጋቸውን በማጅራታቸው ላይ ከግራ ወደ ቀኝ አጋድመውና የበቅሎዋን ልጓም በረጅሙ በቀኝ እጃቸው ይዘው ወደፊት እየሳቡ፤ “…. ደሴ ታዋቂው የማሪቱ ለገሰ ቤት ነበር። እኔም ደንበኛ ነበርኩ። አንድ ቀን ገና ከመንገድ እንደመጣሁና አቧራ እንደለበስኩ ገብቼ ከቡና ቤቷ ተሰየምኩ። ማሪቱ እዚህም እዚያም የተቀመጡትን እየተዟዟረች በማሲንቆ ታጅባ ታሞጋግሳለች። ሃብታምና የዘነጡ ሰዎች ይበዛሉ። እኔ ገብቼ ገና እንዳየችኝ አመድ መምሰሌን ታዝባ ኖሯል። ከማዶ ወደተቀመጠው ሰውዬና ወደኔ እያመላከተች እንዲህ ስትል ተነኮሰችኝ።
እዪት የጅማ ልጅ ከረባቱን አስሮ
መጣ የወሎ ልጅ የወር እብድ መስሎ
ደንበኞች ሁሉ በሳቅ አውካኩ። ጸጉሬ የእብድ መስሎ መንጨባረሩንና አቧራ መልበሴንስ እኔም ቀድሜ ልብ ብያለሁ። አብሬ ሳቅኩ። ግን አለባበሴንና የጸጉሬን አቧራ መልበስ ሊያስረሳልኝ የሚችለው ምን እንደሆነ አውቃለሁ። ገንዘብ ነው። ቆየት ብዬ የቤቱን ሰው ሁሉ ከበር መልስ መጋበዝ ጀመርኩ። ውስኪ አወረድኩና ፀጉሬን እዚያው ሰው መሃል ታጠብኩበት። ቤቱ ተንጫጫ። ሁሉም ስለተጋበዘ አጨበጨበ። ማሪቱም በተራዋ ተጋብዛና ተዝናንታ ስታበቃ ወደ እኔ መጣችና የቅድሙን ስድብ እንዲህ ስትል አካካሰች።
ተሳስቼ ኖራል ጅስሙን ተመልክቼ
ተሳስቼ ኖሯል ከረባት አይቼ
ምን ያረግልኛል ከረባት አሳሪ
ይምጣ የወሎ ልጅ ባውንድ ዘርዛሪ
ቤቱ በድጋሚ በጭብጨባ በአንድ እግሩ ቆመ። ሁሉም አውካካ። አየህ ልጄ፤ ወጣት ሆኜ ያሳለፍኩት ህይወት እንዲህ ያለ ስለነበር ነው ልጆቼን በየቦታው የወለድኳቸው። አላሳደኳቸውም’ንጂ። አብዛኞቹ ትልልቅ ልጆች የተወለዱት ከዚያ ዘመን ጀምሮ ስለነበር በየቦታው፣ በየደረስኩበት ሁሉ ነበር። በመቀጠል ደግሞ በደርግ ጊዜ ከሶማሊያ ወረራ ጀምሮ ለሰባት አመት ያህል በወታደርነት ስላገለገልኩ፣ የተወሰኑት የወታደር ልጆች ናቸው ማለት ነው። ከወለድኳቸው አስራ ሁለት ልጆች ያሳደኩት አምስቱን ብቻ ነው። መቼም የአላህ ስራው ግሩም ነው፤ ከሸመገልኩና ገንዘቤን ከበተንኩ በኋላ ልብ ገዝቼ ተቀመጥኩ። ከዚያ ወዲህ ያሉትን ልጆቼን በስርዓት አሳድጌያለሁ።”
እንዲህ እንዲህ እያልን ጉዟችንን ቀጠልን። የሃጂ እውቀትና ታሪክ ተወርቶም ተሰምቶም አያልቅም። ጨዋታቸው ሳይቋረጥ ከመድረሻችን ደረስን። ከመንደራቸው አካባቢ ስንደርስ ከተሰበሰቡት ከብቶች መሃል ቡሬዋን እያሳዩኝ፤ “አየህ አይደል ቡሬ ላምህ ወልዳልሃለች። ባለፈው የተላከልህ ቅቤም ከእርሷ የተገኘ ስለሆነ የራስህ ነው ማለት ነው። ይልቅ ወይ ሽጥና ገንዘቡን ውሰድ ወይ ደግሞ ለእረኛ የእርቢ ስጥና የእኩል ተካፈል፤ አሁን እረኛ እየጠፋ ስለሆነ ተቸግሬያለሁ…” አሉኝ፤ ወደ መንደሯ እየመሩኝ።
ከሁለት አመት በፊት በስጦታ ያበረከቱልኝን ቡሬ በአካል መጥቼ አየኋት። በበጎነት የተጀመረው የዝምድና ጉዞ ቤተሰብ አስገኝቶ ቀጥሏል።

Read 407 times