Friday, 03 May 2024 00:00

ትላንት በፖሊስ ተይዘው የተወሰዱት 2 የማሕበረ ቅዱሳን አመራሮች ዛሬ ከእስር መለቀቃቸው ተሰማ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በትላንትናው ዕለት በፖሊስ ተይዘው የተወሰዱ ሁለት የማሕበረ ቅዱሳን አመራሮች በዛሬው ዕለት ከእስር ተፈተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸው ተሰምቷል፡፡ አመራሮቹ  በፖሊስ የተያዙትና የተወሰዱት  ከመኖሪያ ቤታቸው እንደነበር ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን፣ ሰንበት ትምሕርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ (ማሕበረ ቅዱሳን) ሰብሳቢ የሆኑት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም እና የማሕበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መምህር ዋሲሁን በላይ፣ ትላንት በፖሊስ ተይዘው ሜክሲኮ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ መወሰዳቸውን ማሕበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ዘግቦ ነበርለ፡፡  

የሁለቱ አመራሮች መኖሪያ ቤት በትላንትናው ዕለት በፖሊስ የተፈተሸ ሲሆን፤ አመራሮቹ ተይዘው የተወሰዱበት ምክንያት እስካሁን  አልታወቀም፡፡

በተያያዘ ዜና፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ሊቀ ማእምራን ብርሃኑ ተክለያሬድ ባለፈው ሳምንት  ሐሙስ ከመኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ ተይዘው መወሰዳቸው ተነግሯል።

ባለቤታቸው ወይዘሮ ኢየሩሳሌም ተስፋው በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መረጃ፤ መሪጌታ ብርሃኑ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከማለዳው 12 ሰዓት ላይ ነበር፡፡ ሊቀ ማእምራን “ለጥያቄ እንፈልግዎታለን” ተብለው ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደተወሰዱ ነው ባለቤታቸው ባጋሩት መረጃ  የጠቆሙት፡፡

ሊቀ ማእምራን ብርሃኑ፣ ከሳምንታት በፊት በቋሚ ሲኖዶስ ፈቃድ፣ የደቡብ አፍሪካ አሕጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተደርገው መዘዋወራቸው ታውቋል፡፡

Read 574 times