Monday, 29 April 2024 07:36

የሃገሬ ሰዎችና የመጽሐፍ ቀን!

Written by  የአብፀጋ ተመስገን / Maddbn
Rate this item
(4 votes)

 እኔ ብዙ መጽሐፍትን አንብቤያለሁ፤ ያሳብዳሉ የተባሉትንም ጭምር ፤ እንግዲህ አሳብደውኝ እንደሆን አንተ ምስክር ነህ። ማንበብ አያሳብድም ! ያበዱ ካሉም መጽሐፎቹ ሳይሆኑ ፤ የአንባቢዎቹ የመረዳት መጠንና አስቀድሞ በውስጣቸው ለእብደት የሚያበቃ እርሾ ስለነበረ ፤ ወይም ደግሞ ያነበቡትን ሁሉ በህይወቴ ልተርጉመው ካሉ ነው ችግሩ፡፡”
  

         ቀሽሞች ማንበብ ያሳብዳል፣ ለወፈፌነት ይዳርጋል ... ወዘተ ገለመሌ። በዚህ ሸውራራ እሣቤ የወለደው አሉባልታ የሚያምኑ የሀገሬ ሰዎች፣ ማንበብ ምሉዕ እንደሚያደርግ ከሚስማሙቱ  በቁጥር ሣያመዝኑ እንደማይቀርም ይገመታል።
“ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” የተሰኘው ብሂል፤ ከ”ማርፈድ የስንፍና ምልክት ነው”  በመቀጠል ዝነኛ ነው። በሀገራችን ትምህርት ቤቶች ግድግዳዎች ላይም በብዛት ሠፍሯል። የማርፈዱን ጥቅስ ተደግፎ አለንጋውን እየወዘወዘ በሚጠብቀን መምህር፣ እግራችን ለለገመው መዳፋችንን የተለበለብንም ቁጥር ስፍር የለንም። ሁላችንም ግን ሰነፍ አልነበርንም። ከዚያ ይልቅ መዘግየታችን ስለ ስንፍናችን ከመሰከረ ዱላው ለምን አስፈለገ ... ስንፍና ያስገርፋል ማለት ነው ? እያልን ፍልስፍና ... ተብሰልስሎት ቢጤ የሚዳዳን ነበርን።
 ለመጎበዝ ከጣርንም ፤ ዱላ ፣ ቁጣና ተግሳጽን መሠል፣ አቀራረባቸውን የሣቱ አስቀያሚ ነገሮች ሽሽት፣ የሚፈልጉት አይነት ጎበዝ ሆኖ ለመሸወድ እንጂ ፤ ውስጣችን በጠራን መንገድ ጥሩ ተጉዘን አልነበረም። እልፍ ገፅ ኖሮን ሣለ አንድ መልክ ይዘንላቸው እንደ ሰብል ሊያመርቱን ነበር የሚታገሉት። የፀደቀላቸውን የዝንተ ዓለም መመዘኛ አድርገውት ፤ እንደራሱ  ያንሰራራውን እሱን አልመሰለም በሚል መመዘኛ አበባውን አረም እያሉ ሲነቅሉብን ነው የከረሙት። ከዛ መሀል ያመለጥነው ታዲያ በንባብ ነው !
 የመጽሐፍ ገፆች አቅፈው ፣ ደግፈውና ሸሽገው አሻገሩን። ንባብ ማምለጫ ነው ! አዳም አይኑን ገልጦ በገላው እንደባነነው  ከራቁታችን መዋሀጃ። ከትቢያው መጪና ያለፈ ማንነት የሚያስተዋውቅ። ከመንጋው አምልጦ ራስን የሚቀላቀሉበት። ንባብ ማምለጫ ነው።
መንጋ ከምንላቸው መሀል ዋነኞቹ ንባብ ያሳብዳል ባዮቹ  ናቸው።  በእርግጥ እድሜና አቅምን ያላማከለ በነሲብ የሚደረግ ጭፍን ንባብ፣ ለአይምዕሮ ጤና መታወክ መነሻ ሠበብ ሊሆን ይችል ይሆናል። ጋሽ ስብሃት ”የሚያሳብዱ መጽሐፍት አሉ የሚባለው እውነት ነው ወይ?” ተብሎ ሲጠየቅ፣ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡፡
"እኔ ብዙ መጽሐፍትን አንብቤያለሁ፤ ያሳብዳሉ የተባሉትንም ጭምር፤ እንግዲህ አሳብደውኝ እንደሆን አንተ ምስክር ነህ። ማንበብ አያሳብድም ! ያበዱ ካሉም መጽሐፎቹ ሳይሆኑ ፤ የአንባቢዎቹ የመረዳት መጠንና አስቀድሞ በውስጣቸው ለእብደት የሚያበቃ እርሾ ስለነበረ ፤ ወይም ደግሞ ያነበቡትን ሁሉ በህይወቴ ልተርጉመው ካሉ ነው ችግሩ፡፡”
ለዚህ ታዲያ የገዛ አስተሳሰባችን እንጂ  ማንበብ እንዴት ተጠያቂ ሊሆን ይችላል ? እንደ’ኔ እጅግ በጣም ወደ ኋላ ለመቅረታችን  ዋነኛው ምክንያት አለማንበባችን ይመስለኛል። ከሰሞኑ በማሕበራዊ ሚዲያ ገፆች ወዲያ ወዲህ ስርመሰመስ ያነበብኩት አስደንጋጭ ዜና፣ በራሱ ምን ያህል መቀመቅ ውስጥ እንዳለን የሚጠቁም ነው።
ዜናው በአጭሩ የሚገልጸው 56 በመቶ የሆኑ የሀገራችን፣ የ2ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች አንድም ቃል ማንበብ እንደማይችሉ የሚገልጽ ነው። አይዟችሁ አትደንግጡ !  ጥናቱ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው 63 በመቶ የማያነቡ ህፃናት ቁጥር በጥቂቱ መሻሻሉንም ይገልጻል፡፡ እንግዲህ አሁናዊ መልካችን ይህን ከመሠለ መጪው ምን ያህል አድካሚ መሆኑን መገመት ቀላል ነው።
ጥንታዊውን የብራና ድጉስ ፅሁፎቻችንን ሣናነሳ፤ በዘመናዊው ህትመት ያስቆጠርነው ዕድሜ ገና ጨቅላ ነው። የመጀመሪያው ልብወለድ በ1900 ዓ.ም የታተመው የነጋድራስ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ ጦቢያ ነው። በ1940 ዓ.ም በተመስገን ገብሬ ተፅፎ የታተመው “የጉለሌው ሠካራም” የመጀመሪያው አጭር ልብ ወለድ ነው። ገና 100 ዓመት እንኳ አልሞላንም፤አጭር ልብወለድ ማሣተም ከጀመርን።
ግሪካዊው አንድሪያ ካቫዲ ምስጋና ይግባውና፣ የመጀመሪያው ጋዜጣ አዕምሮ በ1902 ዓ.ም መነበብ ቢጀምርም ጥቂት ሣይቆይ ከውጭ ሊገባ የነበረው የማተሚያ ማሽን በመዘግየቱ ምክንያት በ1903 ዓ.ም ተቋርጧል። በየመሀሉ ለዓመታት ተቋርጦ እንደገና ስራውን ሲጀምርና ሲያቆም እንደምንም እየተንገዳገደ እስከ ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ድረስ ዘልቆ ነበር።
ዛሬ ላይ  የሚታተሙ መጽሔትና ጋዜጣዎች ቁጥራቸው በቂ አይደለም። የአንባቢ ቁጥር ይጨምር ዘንድ የሚያበረታታና ተስፋ የሚሰጥ ጭላንጭል አሁንም አይስተዋልም። በተቃራኒው በወረቀት ዋጋ መወደድ ምክንያት ራሣቸውን ከገበያው ያገለሉ ማተሚያና መጽሐፍት ቤቶች ብዙ ናቸው።  የመጽሐፍት መወደድም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ሔዶ የሚሰማው ዋጋ ፤ የክፍለ ዘመንና ዓመተ ምህረት አሃዝ እንጂ ለአንድ መጽሐፍ የተተመነ አልመስል ብሏል።
እንግዲህ በዚህ ነባራዊ አቋም እንዲህ ጎድለን ሣለ ነው፤ ያለ እግር ለመቆም የምንጣጣረው።  ”እንኳን አደረሰን“ እየተባባልን የዓለም የመጽሐፍ ቀንን ከመላው ዓለም እኩል የምናከብረው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡
እየጠዘጠዘች ፈገግ የምታሰኘኝን እውነተኛ አጋጣሚ ተንፍሼ ላሳርግ ፤
  ወዳጆቼ በብዙ ድካም ፣ ውጣውረድና መከራ መጽሐፍ አሰባስበው ቤተመጽሐፍ በማቋቋም ለህዝብ ክፍት ያደርጋሉ ... አፍንጫቸው ስር  ቤተመጽሐፍ እንደተከፈተላቸው ዘግይተው የሰሙት የመንደሩ ወጣቶች ያነባሉ ተብሎ ሲጠበቅ ምን ቢሉ ጥሩ ነው ?
እነዚያን ሁሉ መጽሐፍት ተደራጅተው ከመኪና በማውረድ የሚያገኙት ሣንቲም ስላመለጣቸው ተቆጭተው ..”ማን አባቱ ነው ያወረደው ? ! “ አሉ፡፡ ንባብና እኛ እንግዲህ የዚህን ያህል ነን፡፡

Read 211 times