Monday, 29 April 2024 07:22

ምዕራባውያን ፈላስፎች (አልበርት ካሙ)

Written by 
Rate this item
(2 votes)


       ”--ካሙ የሳትረ የቅርብ ወዳጅ ነበር፡፡ ሆኖም ወዳጅነታቸዉ ከዘጠኝ አመት በኋላ በ1952 ዓ.ም ተቋጭቷል፡፡ በሁለቱ መካከል መቃቃር እንዲፈጠር ያደረገዉ ዐቢይ ምክንያት ካሙ በኮሚኒዝም ላይ ያንፀባርቀዉ የነበረዉ ትቸት ነዉ፡፡ አንድሬ ዢድ፣ ሊዮ ቶልስቶይ፣ ፊዮዶር ዶስቶቭስኪ፣ ሄርማን መልቬል እና ፍራንዝ ካፍካ ካሙ ላይ ታላቅ ተፅዕኖ የፈጠሩ ስመ ጥር ልብ ወለድ ደራሲያን ናቸዉ፡፡ --”
               መኮንን ደፍሮ


       (ክፍል አንድ)
ሕይወት እና ሥራዎች
አልበርት ካሙ ፈረንሳዊ ፈላስፋ፣ ልብ ወለድ ጸሐፊ፣ ጸሐፌ ተዉኔት፣ የቴአትር ተዋናይ፣ ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ አክቲቪስት ነበር፡፡ ካሙ ጥቅምት 7 ቀን 1913 ዓ.ም ሞንዶቪ ዉስጥ ከገበሬ ወላጆቹ ተወለደ፡፡ ሞንዶቪ ቦን በተባለ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ውስጥ የምትገኝ ትንሽ የምስራቅ አልጀሪያ ከተማ ናት፡፡
ካሙ ገና ጨቅላ ሳለ ነበር በአንደኛዉ የዓለም ጦርነት አባቱን ሉሲያ ኦጉስት ካሙን በሞት ያጣዉ፡፡ በእዚህም ምክንያት የአደገዉ የእስፔን የዘር ሐረግ ባላት እናቱ ካትሪን ሄለን ስንቴስ እጅ ነዉ፡፡ ስንቴስ ስሟን እንኳ መጻፍ የማትችል መሀይም ነበረች፡፡ ካሙ የልጅነት ጊዜዉን ያሳለፈዉ በአስከፊ ድህነት ዉስጥ ነበር፡፡ በ1932 ዓ.ም አልጀርስ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ፍልስፍና አጥንቷል፡፡ በ1942 ዓ.ም በገጠመዉ የሳንባ ደዌና አልጀሪያ ዉስጥ በነበረዉ የፖለቲካ ጭቆና ምክንያት አልጀሪያን ለቆ ወደ እናት አገሩ ፈረንሳይ አቀና፡፡ ፈረንሳይ ከገባ በኋላ በ1943 ዓ.ም ኮምባት ተብሎ የሚጠራዉንና ፈረንሳዮች የጀርመን ናዚን ወረራ በመቃወም ንቅናቄ ያደርጉበት የነበረዉ ምስጢራዊ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሥራ ጀመረ፡፡ ከእዚህ ጋዜጣ ተሳታፊ ጸሐፍት አንዱ ዠን-ፖል ሳትረ ነበር፡፡
ጁሊያን ያንግ የተባለ የፍልስፍና ምሁር እንደ ገለፀዉ፣ ካሙ መልኩ አሜሪካዊዉን የፊልም ተዋናይ ሃምፕሬይ ቦጋርትን የሚመስል፣ ብዙ ጊዜ ከአፉ ጥግ ሲጋራ የማይጠፋ መልከ መልካም ነበር፡፡ ዘ አፍሪካን ኩዊን በተሰኘዉ የፊልም ሥራዉ ባሳየዉ ድንቅ ትወናዉ፣ በ1952 ዓ.ም ታላቁን የፊልም ሽልማት ኦስካር ያሸነፈዉ ሃምፕሬይ ቦጋርት፤በሲኒማ ታሪክ ስማቸዉ ጎልቶ ከሚጠቀስ ኮከቦች መካከል አንዱ ነዉ፡፡ ካሙ ሸበላነቱም ከሴቶች ጋር በቀላሉ እንዲቀራረብ አግዞታል፡፡ ይህ መልከ መልካም ሰው ለትዳር አጋሮቹ የማይታመን ሴት አውል ነበር፡፡ ካሙ ገና በወጣትነት ዕድሜዉ ጎጆ የቀለሰ ሰው ነበር፡፡ በ1934 ዓ.ም የአስራ ዘጠኝ አመት ወጣት ሳለ የመጀመሪያ የትዳር አጋሩን ሲሞን ሃይን አገባ፡፡ ሆኖም በሚስቱ አመንዝራነት ምክንያት ከአንድ አመት በኋላ ትዳራቸዉ በፍቺ ተቋጭቷል፡፡ ቆይቶ በ1940 ዓ.ም በሃያ ስድስ ዓመቱ ሁለተኛ ሚስቱን ፒያኒስትና የሒሳብ ሊቋን ፍራንሲን ፋዉርን አገባ፡፡ ከእሷ ሁለት መንታ ልጆችን አፍርቷል፡፡    
ካሙ ወደ ሥነጽሑፉ ዓለም እንዲቀላቀል በጎ ተፅእኖዉን ያሳረፈበት የፍልስፍና መምህሩ ዠን ግረነር ነዉ፡፡ ካሙ በሕግ የሚፈፀምን የሞት ቅጣ በፅኑ በማዉገዝ የሚታወቅ ፈላስፋ ነበር፡፡  ካሙ በመጀመሪያ ደረጃ ራሱን ጸሐፊ እንጂ ፈላስፋ አድርጎ አይቆጥርም ነበር፡፡ ይህ ሰው ሥራዎቻቸዉ በዓለም ዙሪያ በስፋት ከተነበቡላቸዉ ዘመናዊ ፈረንሳዊያን ደራሲያን መካከል አንዱ ነዉ፡፡   
ካሙ የሳትረ የቅርብ ወዳጅ ነበር፡፡ ሆኖም ወዳጅነታቸዉ ከዘጠኝ አመት በኋላ በ1952 ዓ.ም ተቋጭቷል፡፡ በሁለቱ መካከል መቃቃር እንዲፈጠር ያደረገዉ ዐቢይ ምክንያት ካሙ በኮሚኒዝም ላይ ያንፀባርቀዉ የነበረዉ ትቸት ነዉ፡፡ አንድሬ ዢድ፣ ሊዮ ቶልስቶይ፣ ፊዮዶር ዶስቶቭስኪ፣ ሄርማን መልቬል እና ፍራንዝ ካፍካ ካሙ ላይ ታላቅ ተፅዕኖ የፈጠሩ ስመ ጥር ልብ ወለድ ደራሲያን ናቸዉ፡፡
ካሙ፣ ገና በጎልማሳነት እድሜዉ በመኪና አደጋ ቢቀጭም፣ እጅግ ታላላቅ የሥነጽሑፍና የፍልስፍና ሥራዎችን ለዓለም አበርክቷል፡፡ ካሙ በ1937 ዓ.ም ያሳተመዉ የወግ ሥራዉ ቢቲዊክስ ኤንድ ቢቲዊን ይሰኛል፡፡ በቀጣዩ ዓመት በ1938 ዓ.ም ያሳተመዉ ሥራዉም ወግ ሲሆን፤ ነፕሾልስ ይሰኛል፡፡ በ1942 ዓ.ም ዘ ስትሬንጀር የተሰኘ የልብ ወለድ ሥራዉን አሳትሟል፡፡ ይህ ሥራ ለህትመት በበቃበት ወቅት ሳትረ ሳይቀር ታላቅ የፈጠራ ሥራ መሆኑን አወድሶ ኂሳዊ መጣጥፍ ጽፏል፡፡ ዘ ስትሬንጀር በብዛት የተሸጠና ከአርባ በላይ ወደ ሆኑ ቋንቋዎች የተተረጎመ የሃያኛዉ ክፍለ ዘመን የፈረንሳይ ልብ ወለድ ነዉ፡፡ የእዚህ ሥራ ዐቢይ ሴማ ወለፈንድ ነዉ፡፡ በእዚሁ አመት ያሳተመዉ ታላቅ የፍልስፍና ሥራዉ ዘ ሚዝ ኦፍ ሲስፈስ ኤንድ አዘር ኢሴይስ ይሰኛል፡፡ ይህ ሥራው ዘ ስትሬንጀር ዉስጥ የዳሰሰዉን ወለፈንድ በጥልቀት የፈከረበት ሥራዉ ነዉ፡፡ በ1944 ዓ.ም ለመድረክ የበቃ የተዉኔት ሥራዉ ክሮስ ፐርፐዝ ይሰኛል፡፡ ካሊጉላ በቀጣዩ ዓመት በ1945 ዓ.ም ለመድረክ የበቃ የተዉኔት ሥራዉ ነዉ፡፡ እነዚህን ሥራዎች ተከትሎ በ1948 ዓ.ም ስቴት ኦፍ ሲይጂ፣ በ1950 ዓ.ም ደግሞ ዘ ጄስት የተሰኙት ሥራዎቹ ለመድረክ በቅተዋል፡፡ በ1947 ዓ.ም ያሳተመዉ ዝነኛ የልብወለድ ሥራዉ ዘ ፕለይግ ይሰኛል፡፡ በ1951 ዓ.ም ዘ ሪቤል፣ አን ኢሴይ ኦን ማን ኢን ሪቮልት የተሰኘዉን ሥራዉን አሳተመ፡፡ በ1956 ዓ.ም ያሳተመዉ ሌላኛዉ የልብ ወለድ ሥራዉ ዘ ፎል ይሰኛል፡፡ ከአንድ አመት በኋላ በ1957 ዓ.ም ኤግዛይል ኤንድ ዘ ኪንግደም የተሰኘ ሥራዉን አሳትሟል፡፡ ካሙ ከሞተ በኋላ በ1994 ዓ.ም በሕይወት ሳለ ጽፎ ያላገባደደዉ የሕይወት ታሪኩ ላይ የተመሠረተዉ የልብ ወለድ ሥራዉ ዘ ፈርስት ማን ታተመ፡፡ ይህ ሥራ ካሙ ላይ የመኪና አደጋ በደረሰበት ወቅት ሳምሶናይቱ ዉስጥ የተገኘ ሥራ ነዉ፡፡ ከእዚህ ድርሰቱ ጋር አብሮ የተገኘው ሌላኛው መጽሐፍ የፍሪድሪክ ኒቼ ዘ ጌይ ሳይንስ ነው፡፡                
ካሙ ለዓለም ሥነጽሑፍ ማለፊያ ሥራዎችን በማበርከቱ  October 16 1957 ዓ.ም ታላቁን የኖቤል ሽልማት በሥነጽሑፍ ተሸልሟል፡፡ ነገር ግን የኖቤል ሽልማትን ከተቀበለ በኋላ በእዚህ ዓለም የኖረዉ ለሦስት ዓመታት ብቻ ነዉ፡፡ ካሙ በተወለደ በአርባ ስድስት አመቱ የጋሊማርድ አሳታሚ ባለቤት ጋስቶኦን ጋሊማርድ ዘመድ ከሆነዉ ጓደኛዉ ሚሼል ጋሊማርድ ጋር ከመኖሪያ መንደሩ ሎርምረን ወደ ፓሪስ በመኪና እየተመለሱ ሳለ፣ በመኪና አደጋ ጥር 4 ቀን 1960 ዓ.ም ከእዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ካሙ እና ሚሼል ጋሊማርድ መኪና በፍጥነት የማሽከርከር ሱስ ነበረባቸዉ፡፡ የካሙ ሥርዓተ ቀብር የተፈፀመው ሎርምረን ውስጥ ነው፡፡  
፩. የሕይወት ትርጉም
የበርካታ ፈላስፎችን ትኩረት ከሳቡ ዐቢይ ፍልስፍናዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሕይወት ትርጉም ነዉ፡፡ ለእዚህ ወሳኝ ፍልስፍናዊ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥተዉ ከተፈላሰፉ ፈላስፎች መካከል አንዱ ካሙ ነዉ፡፡ ካሙ ዘ ሚዝ ኦፍ ሲስፈስ በተሰኘ የፍልስፍና ሥራው እንደሚነግረን፣ ሕይወት ፋይዳ አለዉ ወይስ የለዉም የሚለዉ ጥያቄ ፍልስፍና ሊመልሰዉ የሚገባ እጅግ አንገብጋቢ ጥያቄ ነዉ (ካሙ፣ 1955)፡፡ ለካሙ ከሕይወት ትርጉም ጥያቄ የሚቀድም ወሳኝ ጥያቄ የለም፡፡ ለእሱ የሕይወት ትርጉም ፍልስፍና ሊፈታው የሚገባ ብቸኛው ወሳኝ ተግዳሮት የሆነው ራስን ከማጥፋት ድርጊት ጋር በቀጥታ ስለሚሰናሰል ነው፡፡
ወለፈንድ         
ዘ ሚዝ ኦፍ ሲስፈስ ካሙ የሕይወት ወለፈንድነት ወይም ትርጉም አልባነት ምንጩ ምን እንደ ሆነ እንዲሁም ሕይወት ፋይዳ ቢስ በመሆኑ ምክንያት ራስን መግደል ተገቢ ነዉ አይደለም የሚለዉን ጥያቄ የመለሰበት ፍልስፍናዊ ሥራዉ ነዉ፡፡ ብዙ ጊዜ ግለሰቦች ራሳቸዉን ለመግደል ዉሳኔ ላይ የሚደርሱት የሕይወትን ወለፈንድነት ወይም ከንቱነት ሲረዱ ነዉ (ዊክ፣ 2003)፡፡ ለካሙ ሕይወት ወለፈንድ ነው (ቶዲ፣ 1959)፡፡ ይህ ሐቅ የሰዉ ልጅ ፈፅሞ ሊሸሸዉ የማይችለዉ ሐቅ ነዉ፡፡
እንደ ካሙ እሳቤ፣ የሕይወት ወለፈንድነት ምንጩ በፍፁማዊ ትርጉም ፈላጊዉ የሰዉ ልጅና በፍፁማዊ ትርጉም አልባዉ ሁለንታ መካከል ያለ ግጭት፣ ሞት አይቀሬ ታላላቅ ስኬቶቻችንን ሁሉ በቅፅበት መና አንደሚያደርጋቸዉ መታዘባችን፣ ሁለንታ ለእኛ ትልምና ፍላጎት መልስ አልባ መሆኑን መታዘባችን፣ የሰዉ ልጅ ኅሊና የሁለንታን ምስጢር ለመግለፅ ብቁ አለመሆኑ እና የዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ጨዋታ የሆነዉን አታካቹን የሰርክ ሕይወታችንን መታዘብ ነዉ (ካሙ፣ 1955፤ ቶዲ 1959፤ ኮፕልስተን፣ 1994፤ ደ ሉፕ፣ 1966፤ ዌበር 2018፤ ቤኔት 2001፤ ፎለይ 2008፤ ኮፕልስተን፣ 1956)፡፡ ዮንግ (2003) እንደሚነግረን፣ ለካሙ የሰው ልጅ ሕልውና ትርጉም አልባ የሆነበት ሰበብ፣ የፈጣሪ በህልውና አለመኖር ነው  (ዮንግ፣ 2003)፡፡  
ራስን ማጥፋት      
ካሙ እንደሚነግረን፣ ሰዉ ከሕይወት ከንቱነት ሐቅ ጋር ሲላተም ራስን ማጥፋትን መፍትሄ አድርጎ ይወስዳል (ዮንግ፣ 2003)፡፡ ራስን የመግደል ስሜት ሬስቶራንትን ጨምሮ በማንኛውም ጊዜ ሊፈጠር ይችላል (ካሙ፣ 1955)፡፡ ለመሆኑ ራስን መግደል የሕይወት ፋይዳ ቢስነት ትክክለኛ መፍትሄ ይሆናል? በፍፁም ይለናል ካሙ፡፡ እንደ እሱ እሳቤ፣ ራስን መግደል የሕይወት ፋይዳ ቢስነት ስሜት ትክክለኛ መድኃኒት አይደለም፡፡ በመሆኑም ተግባሩ በፅኑ የሚወገዝ ነው፡፡    
ተስፋ
ለካሙ እንደ ራስን መግደል ሁሉ ተስፋ፣ ቂል ሰው ለወለፈንድ ስሜት ትክክለኛ መፍትሄ አድርጎ የሚወስደው፣ በእውነቱ ግን ትክክል ያልሆነ መፍትሄ ነው (ዊክ፣ 2003)፡፡ ተስፋ ካሙ አበክሮ የሚተቸው የዴንማርካዊዉን ኤግዚስቴንሻሊስት ፈላስፋ ሶረን ኪርክጋርድ ጽንሰ ዐሳብ ነው፡፡ ይህ ጽንሰ ዐሳብ ከሃይማኖታዊ እሳቤ ጋር የተሰናሰለ ሲሆን፤ወለፈንድን ከመጋፈጥ ይልቅ በሰማያዊ ሕይወት ተስፋ ማድረግንና ከፈጣሪ ጋር ህብረት መፍጠርን ይሰብካል፡፡ እንደ ካሙ እሳቤ፣ ተስፋ ለሕይወት ፋይዳ ቢስነት ተግዳሮት ትክክለኛ መፍትሄ ሆኖ መቅረብ አይችልም፡፡ ተስፋ ለካሙ ወለፈንድን የመሸሽ ተግባር በመሆኑ የተወገዘ ነዉ (ዊክ፣ 2003)፡፡ የካሙ ፍልስፍና የሚነግረን፣ በእዚህ ዓለም እየኖርነው ካለነው ሕይወት ውጪ ሌላ ተስፋ የምናደርገው ሕይወት አለመኖሩን ነው፡፡ ለካሙ፣ ተስፋ ፍልስፍናዊ ራስን ማጥፋት ነው፡፡ ለምን ቢባል ምክንያታዊነትን መግደል ስለሆነ (ዮንግ፣ 2003)፡፡
ከላይ እንዳየነው ለካሙ ራስን ማጥፋትም ሆነ ተስፋ ለወለፈንድነት ስሜት ትክክለኛ መፍትሄዎች አይደሉም፡፡ ታዲያ እውነተኛ መፍትሄው ምንድር ነው? ካሙ እንደሚነግረን፣ የወለፈንድነት ስሜት ትክክለኛው መፍትሄ አድማ ነው፡፡ ይህን ጽንሰ ዐሳብ በቀጣዩ ጽሑፍ እናያለን፡፡            
ከአዘጋጁ፡-
መኮንን ደፍሮ ልብወለድ ጸሐፊ፣ ገጣሚ እና የሥነ ጽሑፍ ኀያሲ ነው፡፡ የባችለር ድግሪውን በ2009 ዓ.ም፣ የማስተርስ ድግሪዉን ደግሞ በ2015 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና አግኝቷል፡፡ በተማረው የሙያ መስክ በጅማ፣ በመቐለ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሠርቷል፡፡ ጸሐፊው አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጨምሮ በተለያዩ መጽሔቶች ግጥሞቹንና የልብ ወለድ ሥራዎቹን አሳትሟል፡፡      መኮንን በርካታ የኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ሥራዎች ላይ ኂሳዊ መጣጥፎችን ጽፏል፡፡

Read 447 times