Sunday, 28 April 2024 21:20

ኢትዮጵያ ወደ ፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(3 votes)

• 69 እጩ ኦሎምፒያኖች ተመርጠዋል፡፡
    • ሚኒማ ያሟሉ 35 ናቸው፤ 34 አትሌቶች 6 ሳምንት ይቀራቸዋል፡፡
    • በሴቶች ጠንካራ ስብስብ አለ፤ በ5ሺና 10 ሺ የመጨረሻውን ቡድን ለመለየት ፈታኝ ነው።
    • በወንዶች በመካከለኛና በረጅም ርቀት ሚኒማዎች አጥጋቢ አይደሉም፤ በ3ሺ ሜ መሠናክል የተሻለ ምልመላ ተደርጓል።
    • አጠቃላይ ዝግጅቱ ተግዳሮቶች ገጥመውታል፡፡
    • የኦሎምፒክ ኮሚቴ እስከ 213 ሚሊዮን ብር በጀት ያስፈልገዋል። የኦሎምፒክ ችቦው ከመቀሌ ከተነሳ ወር አልፎታል ። ንቅናቄው አዲስ አበባ        ላይ ሐምሌ 6 ያበቃል፡፡
    • የዓለም አትሌቲክስ ለወርቅ ሜዳሊያ 50ሺ ዶላር ይሸልማል፡፡


         69 እጩ ኦሎምፒያኖች ተመርጠዋል
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ለሚሰለፈው የኢትዮጵያ ቡድን   የተመለመሉ እጩ ኦሎምፒያኖችን የስም ዝርዝር በሳምንቱ መግቢያ ላይ አስታውቋል። ፌዴሬሽኑ  በምርጫ ሂደቱ ላይ  በኦሎምፒክ ሚኒማ ማሟያ ወቅት በተካሄዱ ውድድሮች አትሌቶች ያስመዘገቧቸውን ሰዓቶች ዋንኛ መስፈርት አድርጎታል። በሁለቱም ጾታዎች በ5ሺ እና 10ሺ ሚኒማ ያሟሉ አትሌቶች በቂ ብዛት አላቸው። በመካከለኛ ርቀትና በ3ሺ ሜትር መሰናክል ግን በወንድም በሴትም ሚኒማውን ያሟሉ አንዳንድ አትሌቶች ቢኖሩም የኦሎምፒክ ተሳትፏቸውን ለማሳካት ከ50 ቀናት ያነሰ ጊዜ የሚቀራቸው አትሌቶች  በዝርዝሩ ውስጥ ተጠቅሰዋል። የሚኒማ ማሟያ ወቅት ሆኖ የተቀመጠው ከሐምሌ 2023 እስከ ሰኔ 2024 ሲሆን የእጩ ኦሎምፒያኖች ምልመላ ላይ ቅሬታ ያላቸው በሳምንት ጊዜ ውስጥ ማመልከት እንደሚችሉም ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ 6 የውድድር ወደቦች እንደምትሳተፍ ይጠበቃል። በሁለቱም  ፆታዎች የምትወዳደርባቸው ርቀቶች 800 ሜ፣ 1500 ሜ ፣ 3ሺ ሜ መሠናከል፣ 5ሺ ሜ፣ 10ሺ ሜ  ፣ማራቶንና የርምጃ ውድድሮች ይሆናሉ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋ ባደረገው ጊዚያዊ ዝርዝር ላይ በተጠቀሱት የውድድር መደቦች 69 ኦሎምፒያኖች ስማቸው ተጠቅሷል። ከመካከላቸው  በቀሩት 6 ሳምንታት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሚኒማውን ያሟሉት 18 ሲሆኑ የተቀሩት አትሌቶች ሚኒማ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።
 በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ቡድን ጊዜያዊ ዝርዝር ላይ በሴቶች ምድብ ጠንካራ ስብስብ ተይዟል። በ800 ሜትር የዓለምና የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነችው ፅጌ ድጉማ ግንባር ቀደም ሆና ስትጠቀስ ፤ ሐብታም አለሙ በ2024  እንዲሁም ወርቅነሽ መለሠ በ2023 አጋማሽ ላይ ባስመዘገቡት ሰዓት የኦሎምፒክ ሚኒማቸውን አሳክተዋል። ፅጌ ግርማ፣ አዳኑ ነኔኮና ነፃነት ደስታ ሚኒማቸውን ሳያሳኩ በጊዜያዊ ዝርዝር ውስጥ የገቡ ናቸው። በ1500 ሜ ሴቶች ድርቤ ወልተጂና ሒሩት መሸሻ በ2023 አጋማሽ ላይ ባስመዘገቧቸው ሰዓቶች ብርቄ ሐየሎምና ሳሮን በርሔ በ2024 ባስመዘገቡት ሰዓት ወደ ጊዚያዊ ቡድኑ ሲጠሩ፤ ሐዊ አበራና አይንአዲስ መብራቱ ሚኒማ ማሟላት የቀራቸው አትሌቶች ናቸው። በሴቶች 3ሺ ሜትር መሠናክል ሲምቦ አለማየሁና ሎሚ ሙለታ ሚኒማውን በማሟላት ሲያዙ ሚኒማውን እስኪያሳኩ በዝርዝር ውስጥ የገቡት ሌሎቹ 3 አትሌቶች ደግሞ ፍሬህይወት ገሠሠ፣ አይናለም ደስታና እመቤት ከበደ ናቸው። በ5ሺ ሜትር ሴቶች ከ2023 አጋማሽ ጀምሮ ሚኒማቸውን ያገኙ 8 አትሌቶች በጊዚያዊ ዝርዝሩ ውስጥ የገቡ ሲሆን ለተሰንበት ግደይ፣ መዲና ኢሳ ፣እጅጋየሁ ታየ ፣ፍሬወይኒ ሐይሉ፣ ለምለም ሐይሉ፣ አያል ዳኛቸው፣ መልክናት ውዱና ሰናይት ጌታቸው ናቸው። በሴቶች 10ሺ ሜ ላይም በተመሳሳይ 8 አትሌቶች ሚኒማቸውን በማሟላት ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን ጉዳፍ ፀጋይ፣ ፅጌ ገብረሰላማ፣ ሚዛን አለም፣ ግርማዊት ገብረእግዝሔር፣ ቦሰና ሙላቴ ፣ ያለምዘርፍ የኋላው፣ ፎተይን ተስፋውና ሰንበሬ ተፈሪ ናቸው። በመጨረሻም በሴቶች የርምጃ ውድድር ሚኒማ ማሟላት እየቀራት ስንታየሁ ማስሬ ወደ ቡድኑ ተጠርታለች።
በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ቡድን ጊዜያዊ ዝርዝር ላይ በወንዶች ምድብ በ800 ሜ እና በ1500 ሜትር 12 አትሌቶች የተያዙ ቢሆኑም ሁሉም የኦሎምፒክ ሚኒማዎችን ማምጣት የሚጠበቅባቸው ናቸው። በ5ሺ ሜትር ሐጎስ ገ/ህይወትና ጥላሁን ወልዴ አስፈላጊውን ሚኒማ አሟልተው ሲገኙ፤ ኩማ ግርማ ፣ ገመቹ ዲዳ፣ አሊ አብዱልማና፣ አዲስ ይሁኔና ዳዊት ወልዴ ሚኒማቸውን እስኪያገኙ በጊዜያዊነት የተመለመሉ ናቸው።  በ10ሺ ሜትር የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ በሪሁ አረጋዊና ዮሚፍ ቀጀልቻ ሚኒማውን በማሳካት የተያዙ ናቸው። ይስማው ድሉ፣ ታደሰ ወርቁ ፣ ቦኪ ድሪባ፣ በረከት ዘለቀና ሞገስ ጥዑማይ ሚኒማ የማሟላት ዕድል ይዘው ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል። በወንዶች 3ሺ ሜ መሰናክል ጠንካራ ቡድን የተመለመለ ሲሆን ሚኒማውን አሟልተው የተጠሩት አትሌቶች ለሜቻ ግርማ ፣ አብርሐም ስሜ፣ ሳሙኤል ፍሬውና ጌትነት ዋለ ሲሆኑ ሳሙኤል ድጉና ኃይለማርያም አማረ ሚኒማ ማሣካት የሚቀራቸው ናቸው። በወንዶች የርምጃ ውድድር ምስጋና ዋኩማ  ብቸኛው ተመራጭ ሆኗል።
የማራቶን  ቡድን ምርጫው ፈታኝ ይሆናል
በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ቡድን ጊዜያዊ ዝርዝር ላይ በሁለቱም ፆታዎች የማራቶን ቡድኑ እጩ ኦሎምፒያኖች በይፋ አልተገለፀም። ከ2023 አጋማሽ አንስቶ በመላው ዓለም የተካሄዱ ማራቶኖችን ውጤት በመንተራስ ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ ምርጥ ቡድን ለማሰለፍ እንደምትችል መገመት ይቻላል። በፓሪስ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስኬት እንደምታገኝ የሚጠበቀውም በማራቶን ውድድር ነው።
የኦሎምፒክ ማራቶን ቡድን ለመምረጥ በ2023 እና በ2024 በታላላቅ ማራቶኖች ላይ ተመዘገቡ ውጤቶችንና ፈጣን ሰአቶችን ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል። በ2021 ቶክዮ ላይ ለተካሄደው 32ኛው ኦሎምፒያድ የማራቶን ቡድን የተመረጠው በአስገራሚ የማጣርያ ውድድር እንደነበር ይታወሳል። ሱልልታ ላይ በ35 ኪ.ሜ የማራቶን ማጣርያ ውድድር ተዘጋጅቶ የኦሎምፒክ ተወዳዳሪዎች ተመርጠዋል።
ዘንድሮ ከኢትዮጵያ የማራቶን ሯጮች መካከል ከ100 በላይ ሚኒማ ያሟሉ ይገኛሉ። በወቅታዊ ብቃትና ውጤት የተቀመጡትን ዋንኛ መስፈርቶች በማሟላት የቦስተን ማራቶንን ያሸነፈው ሲሳይ ለማ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ይሆናል። ባለፉት ሁለት ኦሎምፒኮች በሪዮ ዲጀኔሮና በቶኪዮ ላይ በማራቶን ለኢትዮጵያ ለመሰለፍ ፈልጎ ያልተሳካለት ቀነኒሳ በቀለ ዘንድሮ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ውጤት ይህን እድል ለማግኘት ይፈልጋል። በ2023 እ.ኤ.አ በቫሌንሽያ ማራቶን ያስመዘገበው ውጤት፣ በለንደን ማራቶን 2ኛ ደረጃ ማግኘቱ እና በማራን የምንጊዜም 3ኛውን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቡ ዋንኛ እጩ ሊያደርገው ይችላል።
ለፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ በወንዶች ምድብ በማራቶን ለመሰለፍ ብቁ የሆኑ ከ10 በላይ አትሌቶች መዘርዘር ይቻላል። የኒዮርክ ማራቶን አሸናፊው ታምራት ቶላ፤ በዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ የወሰደው ልዑል ገ/ስላሴ፣ … ተጠቃሾች ናቸው።
በሴቶች ምድብም ለኢትዮጵያ ማራቶን ቡድን ብቁ የሆኑት እትሌቶች ጥቂት አይደሉም። በ2024 የለንደን ማራቶን ሁለተኛ ደረጃ ያገኛቸውና የኢትዮጵያን የማራቶን ሪከርድ የያዘችው ትግስት አሰፋ፤ የዓለም ሻምፒዮኗ  አማኔ በሬሶ ዋናዎቹ እጩዎች ናቸው። በዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ የወሰደቸው ጎተይቶም ገ/ስላሴ፣  የዱባይ ማራቶን አሸናፊዋ ትግስት ግርማ ሌሎቹ እጩዎች ናቸው።

የኦሎምፒክ ኮሚቴ እስከ 213 ሚሊዮን ብር በጀት ያስፈልገዋል።
አጠቃላይ ዝግጅቱ ተግዳሮቶች ገጥመውታል
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በፓሪስ 2024 ላይ የተሳካ ተሳትፎ ለማድረግ እስከ 213 ሚሊዮን ብር በጀት ያስፈልገዋል። ከወር በፊት የኦሎምፒክ ችቦው በመቀሌ ከተማ ተለኩሶ የኦሎምፒክ ንቅናቄው የተጀመረ ሲሆን ችቦው ወደ ሁሉም ክልሎች ጉዞ በማድረግ ሐምሌ 6 ቀን በአዲስ አበባ ፍፃሜው እንደሚሆን ታውቋል፡፡ ከሳምንት በፊት የኦሎምፒክ አጠቃላይ ዝግጅት ዙሪያ በተዘጋጀው መድረክ ላይ እንደተጠቆመው አጠቃላይ የኦሎምፒክ ዝግጅት ተግዳሮቶች ገጥመውታል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ የተጠሩ እጩ ኦሎምፒያኖች በቀጣይ ሳምንት በሆቴል ተሰባስበው ዝግጅት እንደሚጀምሩ አስታውቋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለኦሎምፒክ የሚደረገው መሰናዶ ከኦሎምፒያድ ወደ ኦሎምፒያድ ከችግር ተላቆ አያውቅም። ዘንድሮም ማናጀሮች፤ አሰልጣኞችና አትሌቶች ስለዝግጅታቸው የኦሎምፒክ አመት ላይ ማማረሩን ገፍተውበታል። የስፖርት መሰረተ ልማት እጦት የአዲስ አበባ አየር ሁኔታ መዛባትና አለመመቸት፤ በአትሌቶች፣ በአሰልጣኞችና በማናጀሮች መካከል ተግባብቶ አለመስራት፤ በስልጠና ሂደት እንደ ብሔራዊ ቡድን ተጋግዞ አለመዘጋጀት ከተግዳሮቶቹ መካከል የተጠቀሱ ናቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሎምፒክ ቡድኑ ፓሪስ ላይ የመለማመጃ ስታዲዮም ፈቃድ ያገኘበትን ስምምነት ከፈረመ ወራት ተቆጥረዋል። እቅዱ አቶኒ ከተባለ ስፍራ በሚገኝ ስታዲዮም የመጨረሻ ዝግጅቱን ለማድረግ ነው። የኦሎምፒክ መድረክ የአገር ገፅታን ለመገንባትና ለማስተዋወቅ  በጣም ትልቅ ቦታ አለው። በ4 ዓመት አንድ ጊዜ የሚመጣ ውድድር እንደመሆኑ ከፍተኛ ዝግጅት መሳተፍ ያስፈልጋል።  አትሌቲክሱን በአገራችን ላይ ለማሳደግ እና አዲስ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል ውጤት በኦሎምፒክ ላይ እንዲመዘገብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተረባርበው መስራት ይኖርባቸዋል።  ከዚህ የተነሳ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለኦሎምፒክ እጩ የምንላቸው ብዙ አትሌቶች አሏት። የኦሎምፒክ ቡድን ሲመረጥ የአትሌቶች ወቅታዊ ብቃት እጅግ ወሳኝ ቢሆንም ምቹ የዝግጅት እቅድ ትብብርና አንድነት አስፈላጊ ነው።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ላይ ለሽልማት የመደበው
ከ2.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሲሆን  በሩጫና በሜዳ ተግባራት የወርቅ ሜዳሊያ ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ብቻ ለእያዳንዳቸው የ50 ሺሕ ዶላር ሽልማት እንደሚያበረክት ይፋ አድርጓል፡፡



________________________________________________  



       እንኳንስ አዲስ ታሪክ ለመስራት ፤ ያለፈውን ለመድገም እየከበደ መጥቷል፡፡
ባለፋት 3 ኦሎምፒያዶች በ5ሺ፣ በ10ሺና በማራቶን ፍፁም የበላይነት ማሣየት ያልተቻለ ሲሆን በ800 ሜ፤ በ1500ሜ እና በ3ሺ ሜ መሠናከል የወርቅ ሜዳሊያ  ውጤት አልተሳካም።
የኦሎምፒክ የስታትስቲክስ መዝገብ እንደሚያመለክተው በወንዶች 800ሜ እና 1500ሜ ምንም አይነት የሜዳልያ ውጤት ተመዝግቦ አያውቅም። በ800 ሜ ሴቶች የሜዳሊያ ውጤት የሌለ ሲሆን በ1500 ሜ 1 የብርና 1 የነሐስ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል። በ3ሺ ሜትር መሠናክል የወርቅ ሜዳሊያ ያልተገኘ ሲሆን በወንዶች 1  በሴቶች 1 የብር ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል።
በ10 ሺ ሜትር በወንዶች 6 የወርቅ፣ 3 የብርና 1 የነሐስ ሜዳሊያዎች እና በሴቶች 5 የወርቅ፣ 2 የብርና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል። በ5 ሺ ሜትር በወንዶች 3 የወርቅ፣ 1 የብርና 2 የነሐስ ሜዳሊያዎች እና በሴቶች 3 የወርቅ፣ 1 የብርና 5 የነሐስ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል። በማራቶን በወንዶች 4 የወርቅ፣ 1 የብርና 3 የነሐስ ሜዳሊያዎች እና በሴቶች 2 የወርቅና 1 የነሐስ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል።
በኦሎምፒክ የምንጊዜም ከፍተኛ ውጤት የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ኢትዮጵያ ከዓለም 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።  23 የወርቅ፣ 12 የብርና 23 የነሐስ ሜዳሊያዎች ፤22 የኦሎምፒክ ዲፕሎማዎች በ4ኛ ደረጃ፣ አምስተኛ ደረጃ 9 ጊዜ፣ ስድስተኛ 14 ጊዜ፣ ሰባተኛ 5 ጊዜ ፣ ስምንተኛ 7 ጊዜ በአጠቃላይ ከ1-3 ባለው ደረጃ 58  ጊዜ በመውጣት በ611 ነጥብ ነው። በወንዶች ኢትዮጵያ ከዓለም 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
13 የወርቅ፣ 7 የብርና 12 የነሐስ ሜዳሊያዎች ፤11 የኦሎምፒክ ዲፕሎማዎች በ4ኛ ደረጃ፣ አምስተኛ ደረጃ 3 ጊዜ፣ ስድስተኛ 10 ጊዜ፣ ሰባተኛ 3 ጊዜ ፣ ስምንተኛ 4 ጊዜ በአጠቃላይ ከ1-3 ባለው ደረጃ 32  ጊዜ በመውጣት በ332 ነጥብ ነው። በሴቶች ኢትዮጵያ ከዓለም 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። 10 የወርቅ፣ 5 የብርና 11 የነሐስ ሜዳሊያዎች ፤11 የኦሎምፒክ ዲፕሎማዎች በ4ኛ ደረጃ፣ አምስተኛ ደረጃ 6 ጊዜ፣ ስድስተኛ 4 ጊዜ፣ ሰባተኛ 2 ጊዜ ፣ ስምንተኛ 3 ጊዜ በአጠቃላይ ከ1-3 ባለው ደረጃ 26  ጊዜ በመውጣት በ279 ነጥብ ነው።

Read 414 times