Saturday, 20 April 2024 12:08

ሠርግ እና የኤልያስ ተባበል በ‹‹ማማዬ››

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

ሙዚቃ ማኅበረሰብን የሚያነቃና የሚያበቃ፤ ሲያልፍም ሕጸጽን ፊትለፊት የሚተችና አንድን ማኅበረሰብ የሚገራ ሲሆን፣ ጥበባዊነቱ ይጎላል፤ ደግሞ ሙዚቃ ሕዝብ ውስጥ ዘልቆ ፋይዳ ካልፈየደ፡- ካላስተማረ፣ ካላዝናና፣

ካላጀገነ፣ ካላበረታታ...ወዘተ. ከጥበባዊነት ይጓደላል፤ ግልጋሎት መስጠት እንዳለበት የማይካድ ሀቅ ነው። ሙዚቃ ከማኅበረሰብ ጋር የተቆራኘ ነው፤ የአንድ ማኅበረሰብ ባሕልን፣ አኗኗርን፣ ትውፊትን፣ ደስታና

ኀዘንን መሸከምና መግለጽ ይችላል።
ኤልያስ ተባበል ባቲ እና አንቺ ሆዬን ከሚዘፍኑ ታላላቅ ዘፋኞች መካከል አንዱ ነው፤ በራስ ቴአትር ተቀጥሮ በሠራበት ወቅት ከባልደረቦቹ ከንዋይ ደበበ፣ ሱራፌል አበበ፣ ተስፋዬ ለማ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ እና ሌሎችም

ጋር አብሮ ተጫውቷል፤ ለዛሬ የተስፋዬ ለማ ግጥምና ዜማ የሆነውን ‹‹ማማዬ›› የተሰኘ ዘፈን በዚህ መልኩ ተዳስሷል፡-
ማማዬን በሁለት ክፍል መዳሰስ ጉዳዩን ቀላል ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ፤
የመጀመሪያው ክፍል፡-
‹‹ማማዬ›› በሚል ዘፈን ባለድምጹ የከጀላትን ኮረዳ ክብደት በሚያባቡ ስንኞች ሲያወጋን እናስተውላለን….
‹‹ከረጅም ማማ ላይ፣ ጥንቅሽ የበላ ሰው፤
ከጎድጓዳ ስፍራ፣ ጠይም የሳመ ሰው፤
እንኳን ሽማግሌ፣ ዳኛም አይመልሰው፤››
ይለናል፤ ከላይ በተሰደሩ ስንኞች ገላ ትዝታ አለ፤ ከፍ ካለም፣ ዝቅ ካለም ቦታዎች ጣፋጭ ቀምሷል፤ ያለፈ ጣፋጭ ታሪኩን እያስታወሰ ለያዥ ለገናዥ የሚያስቸግር ጉብል አለ፤ በአካባቢያችን አንቱታን ያተረፉ

ሸምጋዮችን ለመርታት የሚያበቃ ወኔን ትናንትናው ያላበሰው፤ የአሁን ሁናቴውን ደግሞ እንዲህ ሲል ይነግረናል….
‹‹ደጅ ጠናው፣ ደጅ ጠናው፤
መንገዴም ታከተ፤
የሆዷን ጠይቆ፣ ማን ባሰናበተ፤››
በመጠኑም ቢሆን ጣፋጭ ቀምሶ ኖሯል፤ ይኼንን ሃቂቃ ደግሞ በአደባባይ ናኝቷል፤ በኋላ ቆይቶ ልጅት አሻፈረች፤ ሆኖም ተስፋ አይቆርጥም፤ የሚያስተባብለው ነገር እንደሌለ በእነዚህ ስንኞች ገላ ውስጥ መገንዘብ

ይቻላል….
‹‹አጋሙን ግራሩን፣ ጎዝጉዘው ቢተኙ፤
መች ይጎረብጣል፣ የልብን ካገኙ፤››
አየህልኝ እዚህ ጋር! ከሚወዱት ጋር ሲኮን ቀጋው አልጋ እንዲሆን ዕሙን ነው፤ ጣዕሙን ከሚያውቁት ጋር አብሮ ሲሆኑ ጣመን የለም፤ ሕመምና መታከት እርም ናቸው።
‹‹ቁጣዋ ባልነበር - የመነጫነጯ፤
የውሃ ዳር ሎሚ - ነው ‘ሚመስለው ጉንጯ፤››
በማለት በቁጣና መጎፍላቷ መሃል የማይደበዝዝ ውበቷን በውል ተናዝዟል፤ የጥፊ ምርጓን የሚናፍቅ ተማሪ አለ አይደል እንዴ በአብዬ መንግሥቱ ለማ የግጥም ገላ ውስጥ!
ዝብዝብ እንዳይሆን ወደ ክፍል ሁለት እንስከንተር….
ክፍል ሁለት፡-
‹‹ማማዬ›› የሠርግ ለዛ ያለው ዘፈን ነው ብዬአችሁ አልነበር! በመጀመሪያው ክፍል ደጅ ስለመጥናቱ፣ አብሯት ሊከርም ስለመፈለጉ ይነግረናል - ባለድምጹ፤ በሁለተኛው ክፍል ሁለት ዋና፣ ዋና ጉዳዮችን

ያወጋናል፤
2.1. የትዳር መሥፈሪያው ምን መሆን አለበት?
‹‹ካፈቀሩ እንኳን አይቀር፣ መልካም ጸባይ ያላት መርጠው ያፈቅራሉ፤
ካገቡ እንኳን ላይቀር፣ ዕውቀት የምትሻ መርጠው ያገባሉ፤››
በሚሉ ስንኞች የትዳር መሥፈርት ሊሆን የሚገባው ጸባይና ዕውቀት ሊሆኑ እንደሚገባ ያትታል፤ ቀጥሎ፡-
‹‹ገንዘብ አላት ብሎ፣ መልከ ጥፉ ማግባት፤
ገንዘቡም ያልቅና፣ ሁለተኛው ጣፋት፤››
በማለት በአርቲ-ቡርቲ፣ በፕላስቲክ እና በመሰል ቁሶች ላይ የተመሠረተ ትዳር መውደቂያው ቅርብ እንደሆነ ይናገራል፤
ወዲያው ከላይ ያሉ የትዳር መሥፈሪያዎችን መቃን ያደርጋቸውና፡-
‹‹ዓይነ ቆሎ፣ ሽንጠ ሎጋ - የወለዱ እንደሆን፤
መልካም ጸባይ ያላት፣ የወለዱ እንደሆን፤
ዕውቀት የምትሻ፣ የወለዱ እንደሆን፤
ታመጣለች አማች፣ ብረት መዝጊያ የሚሆን፤››
በማለት ለወላጆች የቤት ሥራ ያኖራል፤ ሴቷም ታላቅ ዕዳ አለባት፤ በአመሏ ብሩክ፣ ወዲህ ሲል ዕውቀትን የቀሰመች፣ ውበትንም ያደላት ካልሆነች የብረት መዝጊያዋ ሲያምራት ይቀራል እንደማለት ነው፤
ቀበል አድርጎ፡-
‹‹በቴስታ በዱላ፣ የሚማታ ከሆን፤
በሆነው ባልሆነው፣ የሚቀና ከሆን፤
የት ወጣች የት ገባች፣ የሚያበዛ ከሆን፤
እንኳን ብረት መዝጊያ፣ ለጭራሮም አይሆን፤››
ሲል ባል ምን ዓይነት ጠባዮችን መላበስ እንዳለበት ትምህርት ያበጃል፤
2.2. የብረት መዝጊያው ነገር
የብረት መዝጊያ አማች ነገር ጣጣ አለበት፤ በአማቾች ዘንድ ቅቡል ለመሆን ወላ የብረት መዝጊያ ለመባል በእነ ኤልያስ ዘመን አባወራው የተቆጠበ፣ ስክን፣ ቅናት የማይነካካው፣ ለሀብት ለንብረቱ ብለው የማይጠጉት

ሲሆን፣ በአሁን ወቅት የብረት መዝጊያ ለመባል እዚህ አንቀጽ ላይ ያለውን በተቃራኒ መተወን አልፎ-አልፎ የግድ ነው፤ በድሮ ትዳር ሴቷም ብትሆን ውብ፣ አዋቂ፣ መልካም ጸባይ ያላት ስትሆን ነው ትዳር

የሚኖራት፤ በአጠቃላይ፣ ‹‹ማማዬ›› ትዳር መፈለግን፣ የትዳር መሥፈርትን፣ የድሮውንና የአሁን ጊዜ ትዳርን የሚያስቃኝ ዘፈን ነው።
ከአዘጋጁ፡-
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ

ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት

ትችላላችሁ።


Read 152 times